የዱባይ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አውሮፕላኖችንና መንገደኞችን በማስተናገድ በአለማችን ከሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች የመጀመሪያውን ደረጃ መያዙን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2014 ዓ.ም 70 ነጥብ 47 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተናገደው የዱባይ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ፣ ከዚህ በፊት በርካታ መንገደኞችን በማስተናገድ ቀዳሚነቱን ይዞ የቆየውን የለንደኑን ሄትሮው አውሮፕላን ማረፊያ በመብለጥ በአንደኝነት መቀመጡን ዘገባው አስታውቋል፡፡
የዱባይ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ስራ አስኪያጅ ሼህ አህመድ ቢን ሰኢድ አል መክቱም እንደገለጹት፣ በርካታ አለማቀፍ በረራዎችን በማስተናገድ የሚታወቀው አውሮፕላን ማረፊያው የሚያስተናግዳቸውን መንገደኞቹን ቁጥር ባለፉት አምስት አመታት በኣማካይ በሁለት ዲጂት እያሳደገ መጥቷል፡፡
አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ዱባይን የአለማቀፍ የአየር በረራ ማዕከል የማድረግ ግቡን ወደ ማሳካት እየተቃረበ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ በተያዘው የፈረንጆች አመትም የመንገደኞቹን ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ፖል ግሪቭስ በበኩላቸው፣ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው አዲስ የበረራ ማስተናገጃ በመክፈት፣ አመታዊ የመንገደኞች ማሰተናገድ አቅሙን በያዝነው የፈረንጆች አመት 90 ሚሊዮን ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በርካታ መንገደኞችን በማስተናገድ በቀዳሚነት ይጠቀስ የነበረው የለንደኑን ሄትሮው አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በ2014 ያስተናገዳቸው መንገደኞች ቁጥር 68.1 ሚሊዮን እንደነበር ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የአፍሪካ ህብረት የአህጉሪቱን ርዕሰ መዲናዎች በመንገድ፣ በባቡርና በአየር በረራ ማስተሳሰር ያስችላል የተባለ ትልቅ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ከቻይና መንግስት ጋር የትራንስፖርት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ከቻይና ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዚያንግ ሚንግ ጋር የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የህብረቱ ሊቀመንበር ንኮሳዛ ድላሚኒ ዙማ፣ ባለፈው ማክሰኞ በአዲስ አበባ የተፈረመውን ስምምነት ህብረቱ እስካሁን ከአጋሮች ጋር ከተፈራረማቸው ስምምነቶች ሁሉ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው ብለውታል፡፡
ዚያንግ ሚንግ በበኩላቸው፤ የመግባቢያ ስምምነቱ የምዕተ አመቱ ትልቅ ሰነድ ነው፣ በአየር በረራ መስክ የተፈረመው ስምምነትም በአፍሪካ ህብረት እና በቻይና መካከል ያለውን ትብብር ወደ አዲስ መስክ ያሰፋ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአንደኛው የአፍሪካ ክፍል ወደ ሌላኛው ለመጓዝ የተሻለ አማራጭ ተደርጎ የሚወሰደው የአውሮፓን የበረራ መስመር የተከተለ አካሄድ ነው ያሉት ሚንግ፣ አህጉሪቱ ሰፊ እንደመሆኗ በአውሮፓ የበረራ መስመሮች ላይ ጥገኛ ያልሆነና አገራቱን በቀላሉ የሚያስተሳስር የራሷ የትራንስፖርት አውታር ሊኖራት ይገባል ሲሉ መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

አሜሪካ በኩባ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳትገባ ያስጠነቀቁት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ራኡል ካስትሮ፤ መሰል ጣልቃ ገብነቶች በሁለቱ አገራት መካከል እንደገና የተጀመረውን ግንኙነት ትርጉም አልባ ያደርጉታል ሲሉ  መናገራቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡ ከ40 አመታት በኋላ ኩባን በመጎብኘት የመጀመሪያው የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ረዳት ጸሃፊ ሮቤርታ ጃኮብሰን ባለፈው ሳምንት አገሪቱን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ራኡል ካስትሮ የአሜሪካ አካሄድ በኩባ ላይ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ማሰቧን ያመላክታል  ብለዋል፡፡
አሜሪካ ይህንን አካሄዷን የማታስተካክል ከሆነ በሁለቱ አገራት መካከል እንደገና የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ትርጉም ያጣል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ አሜሪካ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ለመግባት የምታደርገውን ማንኛውም አይነት ሙከራ አገራቸው በዝምታ እንደማታልፈው አስጠንቅቀዋል፡፡
አሜሪካ በኩባ ውስጣዊ የፖለቲካ ተቃውሞን ለማቀጣጠል እያሴረች ነው ያሉት ራኡል ካስትሮ፣ ይሄም ሆኖ ግን ከዚህ የጣልቃ ገብነት ተግባሯ መታቀብ በምትችልበት ሁኔታ ዙሪያ ከአሜሪካ ጋር ለመምከር ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አገራቸው በኩባ ላይ የጣለችውንና ለአስርት አመታት የዘለቀውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንድታነሳ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪ ያቀረቡት ራኡል ካስትሮ፣ ኩባንያዎቿ በኩባ የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩ የፈቀደችው አሜሪካ፣ በሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች ላይም እንደምትሰራ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

   ቴለር ኤንድ ሰንስ የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ፣ የአገሪቱን ኩባንያዎች የመመዝገብ ስልጣን በተሰጠው ካምፓኒስ ሃውስ የተሰኘ የመንግስት ተቋም ላይ፣ ስሜን ሲመዘግብ የአንዲት ፊደል ግድፈት በመፈጸም ለተለያዩ ቀውሶች ዳርጎኛል ሲል በመሰረተው ክስ የ9 ሚሊዮን ፓውንድ ካሳ እንዲከፈለው ፍርድ ቤት እንደበየነ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ፍርዱ የተላለፈበት የመንግስት አካል በአገሪቱ በኪሳራ ላይ የሚገኙ ተስፋ ቢስ ኩባንያዎችን በሚመዘግብበት ሰነድ ላይ፣ ከስድስት አመታት በፊት በማንችስተር የሚገኝን ቴለር ኤንድ ሰን የተባለ የከሰረ ኩባንያ ለመመዝገብ ፈልጎ፣ በስህተት የአንዲት ፊደል ግድፈት በመፈጸም ቴለር ኤንድ ሰንስ ብሎ በመመዝገቡና መረጃውን ለህዝብ ይፋ በማድረጉ ነው የኩባንያው ሃላፊዎች ክስ የመሰረቱበት፡፡
ኩባንያው ስሙ ተዛብቶ መመዝገቡንና በኪሳራ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳየው መረጃ ለህዝብ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ 250 ሰራተኞቹ ስራ መልቀቃቸውን፣ የብድር አቅራቢ ተቋማትና 3ሺህ ያህል አቅራቢዎችም ከኩባንያው ጋር የነበራቸውን የስራ ግንኙነት ማቋረጣቸውን የኩባንያው ጠበቆች ተናግረዋል፡፡
በምህንድስና ስራ ላይ የተሰማራውና ከ100 አመታት ጀምሮ ወታደራዊ መሳሪያዎችን በማምረት የሚታወቀው  ቴለር ኤንድ ሰንስ ኩባንያ የቀድሞ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፍሊፕ ዴቪሰን ሰብሪ፣ ከስድስት አመታት በኋላ የፊደል ግድፈቱ መከሰቱን ሰምተው ከሁለት ወራት በፊት ከኩባንያው አመራሮች ጋር ስብሰባ ማድረጋቸውንና ክሱን መመስረታቸውን ተናግረዋል፡፡
በእንግሊዙ ሮያል ኮርት ኦፍ ጀስቲስ ፍርድ ቤት ካሳ እንዲከፍል የተወሰነበት የመንግስት ተቋም በበኩሉ፣ የፊደል ግድፈቱን መፈጸሙን ቢያምንም፣ በኩባንያው ላይ ለፈጠረው ስህተት ይሄን ያህል ገንዘብ በካሳ እንዲከፍል የተጣለበትን ቅጣት ተቃውሟል፡፡

ፕሬዚዳንቱና 160 ባለስልጣናት ጥቁር መኪና ትተው ነጭ ሊሙዚን መጠቀም ጀምረዋል

 በመካከለኛው እስያ የምትገኘው ቱርክሜኒስታን፣ የአገሪቱ ዜጎች ከአሁን በኋላ ጥቁር ቀለም ያላቸው መኪኖችን ወደ ግዛቷ እንዳያስገቡ መከልከሏን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የቱርክሜኒስታን የጉምሩክ ባለስልጣናት፣ የአገሪቱ ዜጎች ጥቁር ቀለም ያላቸውን መኪኖች ከውጭ አገራት ገዝተው እንዳያስገቡ የሚከለክል ህግ ከሰሞኑ ይፋ ማድረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለስልጣናቱ ክልከላውን በምን ምክንያት ተግባራዊ እንዳደረጉት ግልጽ አለማድረጋቸውን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣናቱ ከውጭ አገራት መኪና ገዝተው የሚያስገቡ ኩባንያዎችን፣ ከጥቁር መኪኖች ይልቅ ነጭ ቀለም ያላቸውን መኪኖች እንዲያስገቡ እያግባቡ መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው፣ ነጭ ቀለም የመልካም ዕድል ተምሳሌት እንደሆነ መግለጻቸውንም ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉርባንጉላይ በርዲሞሃመዶቭ፤ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ጥቁር መኪና መጠቀም ማቆማቸውንና ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎችም ነጫጭ ሊሙዚኖችን መጠቀም መጀመራቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ እሳቸውን ተከትለውም 160 ያህል የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በነጭ ሊሙዚን መዘዋወር እንደጀመሩ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት የቅንጦት መኪና እንዳይገባ የሚከለክል፣ የተለየ ታርጋ ቁጥር መለጠፍና እይታን የሚጋርድ ሽፋን የተለጠፈባቸውን መኪኖች ማሽከርከር የሚያግድ እንዲሁም ሌሎች ከመኪኖች ጋር የተያያዙ ጥብቅ ህጎችን ማውጣቱንና ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ዘገባው ያመለክታል፡፡

በአለማችን የሚገኙ እጅግ ከፍተኛ ባለፀጋዎች ነገር ሲነሳ የማይክሮሶፍት ኩባንያ መስራቹ አሜሪካዊው ዊልያም ቢል ጌትስ ከሁሉም ቀድሞ ትውስ ቢለን ፈጽሞ አያስገርምም፡፡ ለምን ቢባል? የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊዮነር ነውና፡፡ ዘንድሮም ቢል ጌትስ የዓለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር መሆኑ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህ ባለፀጋ በሀብቱ መጠን ብቻ ሳይሆን በለጋስነቱም የዓለማችን ቁጥር አንድ ሰው ነው፡፡
ዛሬ በዓለማችን እንደ ቢል ጌትስ አይሁን እንጂ የሀብታቸውን መጠን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጥሩ 2325 ቢሊየነሮች ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ሀብት ተጠቃሎ ሲሰላ 7.3 ትሪሊዮን ዶላር  ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ከአሜሪካና ከቻይና በስተቀር የሌሎች የዓለማችን ሀገራትን ጥቅል የሀገር ውስጥ የምርት (GDP) መጠን ይበልጣል።
በዓለማችን የሚገኘው የሀብት መጠን 232.5 ትሪሊዮን ዶላር እንደሆነ ይገመታል፡፡ ከዚህ የዓለማችን የሀብት መጠን ውስጥ 3.1 በመቶ የሚያህለውን የተቆጣጠሩት እነኚህ ባለፀጋዎች ናቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ ከዓለማችን የሀብት መጠን 3.1 በመቶ የሚሆነውን የሚቆጣጠሩት 2325 ባለፀጋዎች ናቸው ማለት ነው፡፡
በአለማችን 3.2 ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከአስር ሺ ዶላር በታች የሆነ ሀብት ሲኖራቸው፣ የእነዚህ ሰዎች ጠቅላላ ሀብት 13.8 ትሪሊዮን ዶላር ይሆናል። ይህ ማለት 3.2 ቢሊዮን የሚሆኑት የአለማችን ህዝቦች ያላቸው ሀብት የ2325ቱን ባለፀጋዎች ሀብት እጥፍ እንኳ አይሆንም ማለት ነው፡፡
በዓለማችን ከሚገኙት 2325 ቢሊየነር ባለፀጋዎች ውስጥ 2039 የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ ሴቶቹ 286 ብቻ ናቸው፡፡ ይህ በመቶኛ ሲሰላ ወንዶቹ 88 በመቶ፣ ሴቶቹ 12 በመቶ ይሆናሉ፡፡
የ286ቱ ሴት ቢሊየነሮች ጠቅላላ ሀብት መጠን 980 ቢሊየን ዶላር ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የዓለማችን 16ተኛ ትልቅ ኢኮኖሚና 252 ሚሊዮን ህዝብ ያላትን የኢንዶኔዢያን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (በ2014 ዓ.ም) በ112 ቢሊዮን ዶላር ይበልጠዋል፡፡
ከእነዚህ 286 ሴት ቢሊየነሮች ውስጥ በራሳቸው ጥረት ቢሊየነር የሆኑት 17 በመቶው  ብቻ ሲሆኑ 75 በመቶ የሚሆኑት ሀብታቸውን ያገኙት በውርስ ነው፡፡
የዓለማችን ቁጥር አንድ ወንድ ቢሊየነር ዊልያም ጌትስ እንደሆነው ሁሉ የዓለማችን ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር የሆነችው ደግሞ ክርስቲ ዋልተን ናት። ዊልያም ጌትስ ቢሊየነር የሆነው በራሱ ጥረት ሲሆን ክርስቲ ዋልተን ግን ቢሊየነር የሆነችው የዎልማርት ኩባንያ መስራች የሳም ዋልተን የበኩር ልጅ የነበረውንና በ2005 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን የባሏን የጆን ዋልተንን ሀብት መውረስ በመቻሏ ነው፡፡

Saturday, 31 January 2015 12:58

የወንዶች የጤና ችግሮች

ወንዶችና ሴቶችን ለየብቻ ፆታ ለይተው የሚያጠቁና ለሞት የሚዳርጉ በርካታ የበሽታ አይነቶች የመኖራቸውን ያህል በሁለቱም ፆታዎች ላይ የሚከሰቱ ሆነው በአንደኛው ፆታ ላይ በርክተው የሚታዩ የበሽታ አይነቶችም አሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 በአሜሪካ ሳይንቲስቶች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ሴቶች እንደ ማይግሪን (ራስ ምታት) ሪህና አስም በመሳሰሉ ከፍተኛ የስቃይ ስሜትን በሚያስከትሉ የጤና ችግሮች ከወንዶች በበለጠ የሚጠቁ ሲሆን ወንዶች ደግሞ ለሞት በሚዳርጉ የበሽታ አይነቶች ይጠቃሉ፡፡ ለዛሬው ወንዶችን ብቻ ለይተው ከሚያጠቁ የበሽታ አይነቶች መካከል ጥቂቶቹን እንመለከታለን፡፡
የታይሮይድ ሆርሞን
በአንገት አካባቢ በሚገኝ አነስተኛ እጢ ውስጥ የሚገኝ ሆርሞን ሲሆን ሆርሞኑ አጠቃላይ የሰውነታችንን የሃይል አጠቃቀም የሚቆጣጠር ነው፡፡ ይህ ሆርሞን ከመጠን በላይ በሚሆን ጊዜ ለእንቅልፍ ማጣት፣ ለልብ ድካምና ለልብ ምት፣ ለክብደት መቀነስ ያጋልጣል፡፡
ሆርሞኑ ከመጠን ባነሰ ጊዜ ወይም ሰውነታችን ከሚያስፈልገው መጠን በታች በሆነ ጊዜ ለስንፈተ ወሲብ፣ ለብልት መወጠር አለመቻል፣ ለዝቅተኛ የወሲብ ፍላጐትና ዘር የመርጨት ችግር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህ ችግር ወንዶችን ብቻ በተናጠል የሚያጠቃ የጤና ችግር ነው፡፡
ፕሮስቴት ካንሰር
ይህ በሽታ ገዳይ ከሆኑና ወንዶችን ከሚያጠቁ በሽታዎች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ ሲሆን በወንዶች የመራቢያ አካል በተለይም በዘር ፍሬዎቻቸው እና ፈሳሽ በሚመነጭባቸው አካላት ውስጥ አላስፈላጊ ህዋሳት ያለ ገደብ ሲራቡ የሚፈጠር የጤና ችግር ነው፡፡ በሽታው በዘር የመተላለፍ እድል ያለው ሲሆን ብዙው ጊዜ እድሜያቸው ከአርባ አመት በላይ በሆናቸው ወንዶች ላይ ጐልቶ ይታያል፡፡
የፕሮስቴት ካንሰር በመጀመሪያዎች የመፈጠሪያ ጊዜው በቴስቶስቴሮን (የወንድ ሆርሞን) አማካኝነት ይነሳና ቀስ በቀስ እድገቱን እየቀጠለ ይሄዳል፡፡
እስከዛሬ በተደረጉ ጥናቶች፤ የበሽታውን መንስኤ ለማወቅ አልተቻለም። ነገር ግን የእድሜ መግፋት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮል መጠጣትና አጫሽነት ካንሰሩን እንደሚያባብሱት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የአለም ጤና ድርጅት ያወጣቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በዓለማችን ከስድስት ወንዶች አንዱ በዚህ በሽታ የመጠቃት እድል ገጥሟቸዋል፡፡ በላይኛው የታፋ አካባቢ ከፍተኛ የህመምና የማቃጠል ስሜት መኖር፣ ቶሎ ቶሎ መሽናትና ሽንት መጣሁ መጣሁ የሚል ስሜት መኖር ለዚህ በሽታ መከሰት ምልክቶች ናቸው፡፡
3. የዘር ፍሬ ካንሰር
እድሜያቸው ከ15-35 ያሉ ወጣቶችን በስፋት የሚያጠቃና በወንዶች የዘር ፍሬ ላይ የሚከሰት የካንሰር አይነት ነው፡፡ የዘር ፍሬ ካንሰር ዛሬ በአለም አቀፍ ደረጃ የበርካታ ወጣት ወንዶች የጤና ችግር እየሆነ ነው። ወንዶች የዘር ፍሬዎቻቸውን በየጊዜው በመዳሰስ እብጠትና ጠጠር ያለ ነገር መኖሩን መመርመርና ጥርጣሬ የሚያሳድር ነገር ከገጠማቸው በአፋጣኝ ወደ ህክምና ባለሙያ ጋ መሄድ እንደሚገባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
4. የጉበት ካንሰር (ሄፓቶሴሉላር ካርሴኖማ)
ይህ በሽታ በሁለቱም ፆታዎች ላይ ሊከሰት የሚችል ቢሆንም ወንዶች በዚህ በሽታ የመጠቃት እድላቸው ከሴቶች በሁለት እጥፍ የበለጠ ነው፡፡ በሽታው ሒፓቶቶሳይት በተባለው የጉበት ህዋስ ላይ ተከስቶ ካደገ በኋላ ቀስ በቀስ አጠቃላይ ጉበትና መላው ሰውነት ላይ እያደገ በመሄድ፣ ለከፍተኛ የጤና ችግርና ለሞት የሚያጋልጥ በሽታ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ብዙ አልኮል በየጊዜው የሚጠቀሙ ሰዎች በጉበት ህብረህዋሳቸው ላይ ቁስለትና ጠባሳ እንዲፈጠር በማድረግ ለጉበት በሽታ ይጋለጣሉ። በሽታው በገዳይነቱ የታወቀና በየዓመቱ በርካቶችን ለህልፈት የሚዳርግ በወንዶች ላይ ጐልቶ የሚታይ በሽታ ነው፡፡
5. ከፍተኛ የደም ግፊት
ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በከፍተኛ የደም ግፊት ይጠቃሉ፡፡ የወንዳ ወንድነት ሆርሞን መጠን በደም ውስጥ ከፍተኛ ሲሆን የደም ግፊት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሥራ አካባቢ ውጥረት፣ የእንቅልፍ እጦትና ጭንቀት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በደም ግፊት በሽታ የበለጠ እንዲጠቁ ያደርጋቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ወንዶች ከሴቶች ይበልጥ በልብ በሽታ፣ በኮሌስትሮል፣ በደም ቧንቧ ችግሮች፣ በመተንፈሻ አካላት ካንሰርና መሰል የጤና ችግሮች እንደሚጠቁ በአሜሪካ ሳይካትሪስት ማህበር የተደረገና ባለፈው ዓመት ይፋ የሆነ ጥናት አመላክቷል፡፡ በአጠቃላይ ሴቶች እጅግ ስቃይ በሚያስከትሉ ህመሞች ወንዶች ደግሞ ለሞት በሚዳርጉ የበሽታ አይነቶች እንደሚጠቁም ጥናቱ አመልክቷል፡፡

Published in ዋናው ጤና

    አንዲት ዝሙት አዳሪ ቤት ተሸንሽኖ አንድ ሜትር ተኩል በሆነ የማያፈናፍን ክፍል ትከራያለች፡፡ ኪራዩ በቀን ወይም በወር አይደለም በሰው ነው፡፡ አንድ ወንድ ሲገባ 5 ብር ትከፍላለች፡፡ ምንም ነገር ከውጭ መግዛት አትችልም፡፡ ለምሳሌ ቡና፣ ለስላሳ፣ ማስቲካ፣ ሲጋራ (የምታጨስ ከሆነ)፣ … መግዛት ብትፈልግ ከአከራዮቿ ነው መግዛት ያለባት፡፡ ከምትቆምበት በራፍ ዞር ካለች ‹ሰው መጥቶ የማገኘውን ብር አሳጣሽኝ› በማለት 5 ብር ያስከፍሏታል፡፡ ይህ ሁሉ በደል የሚፈጸመው እዚሁ በመዲናችን ባሉ ሰፈሮች ነው - ሾላ፣ ሰባተኛ፣ … ነገር ግን ይህኛው ሳያመንና ሳያስጨንቀን በየአረብ አገራቱ በእህቶቻችን ላይ የሚደርሰው ግፍ፣ በደልና ጭቆና ያንገበግበናል … በማለት እንባ እየተናነቀው የተናገረው፣ ፅናት የማኅበራዊና ልማት ድርጅት ሊቀመንበር ብርሃኑ መለሰ ነው።
ብርሃኑ፣ የዲኬቲ ኢትዮጵያ የማህበራዊ ግብይት ኮንዶም ሻጭ (ያንግ ማርኬተርስ) ነው። ወጣቱ፤ ይህን አሳዛኝ ታሪክ ያጫወተን፣ ዲኬቲ ኢትዮጵያ፤ ጋዜጠኞች፣ የኮንዶም ሻጭ ወጣቶች ሕይወት ምን እንደሚመስል ግንዛቤ እንዲያገኙ በዚህ ሳምንት በፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ነው፡፡
ብርሃኑና የሌሎች ማህበራት ያንግ ማርኬተርስ ከዲኬቲ ጋር በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውንና ኮንዶም ሸጠው በሚያገኙት ገቢ ህይወታቸው መለወጡን  ተናግረዋል። ከአባሎቻቸው መካከል ባሳዩት ጥሩ የሥራ ብቃት ዲኬቲ በቋሚ ሠራተኝነት የቀጠራቸውና  በዩኒቨርሲቲና በኮሌጅ ደረጃ የሚማሩ አባላት እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ከዲኬቲ ጋር የሚሰሩ ወጣቶች በተለያዩ ክበባት የተደራጁ ሲሆን ኮንዶም በመሸጥ ኤች  አይቪን በመከላከል፣ የቤተሰብ ምጣኔ ግንዛቤ በመፍጠር፣ በእናቶችና ሕፃናት ክብካቤ ላይ የሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ ክበባት ውስጥ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ዲኬቲ የሚሰጣቸውን ኮንዶም እየሸጡ 75 በመቶውን ለራሳቸው ይወስዳሉ፣ ቀሪው 25 በመቶ ለድርጅቱ ሲሆን ለቤት ኪራይ፣ ለጽህፈት መሳሪያ፣ ለቢሮ ቁሳቁስ መግዣ ስለማይበቃቸው ዲኬቲ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡
ኮንዶም መሸጥ ብቻ ሳይሆን በየት/ቤቱ የአቻ ለአቻ ክበባት በመፍጠር ስለ ኤች አይ ቪና የአባማዘር በሽታዎች፣ ልቅ ወሲብ ስለሚያስከትለው ጉዳትና መታቀብ ስላለው ጥቅም፣ …. ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ስራቸው ብዙ መጥፎ ነገር እንዳጋጠማቸው የጠቀሱት ወጣቶቹ፤ በአባቷ የተደፈረች፣ ት/ቤት ሽንት ቤት ውስጥ የወለደች ልጅ፣ … ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የዲኬቲ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትና የኮንዶም አቅርቦት 50 በመቶ እንደሆነ የጠቀሱት የድርጅቱ አገር አቀፍ የችርቻሮ ሽያጭ ማናጀር አቶ ፋሲል ጉተማ፤ ኮንዶም ኤችአይቪ ከመከላከሉም በላይ በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች በመከላከል፣ አዳዲስ የኤችአይቪ በሽተኞች ቁጥር መቀነስ የጤና ግብአት እንደሆነና ከሚጠብቁት በላይ ውጤት ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
ወደፊት ያንግ ማርኬተሮች ከኮንዶሙ ጋር የሚዋጥ የወሊድ መከላከያ፣ የኑትሪሽን ምርቶችና ለምለም (ኦአርኤስ) የተባለውን መድኃኒት ከኮንዶም ጋር እንዲሸጡ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው አቶ ፋሲል ገልጸዋል፡፡


Published in ዋናው ጤና

     ፊፋ የዓለም  እግር ኳስ የተጫዋቾች ዝውውር ሪፖርትን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ሪፖርቱ እንዳመለከተው በ2014 እኤአ  በዓለም እግር ኳስ 13090 ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ያሳተፉ  ግብይቶች ነበሩ፡፡  ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ እንደሆነም ታውቋል፡፡  የተጨዋቾች ብዛትና ዋጋ እድገት ማሳየቱን የገለፀው ሪፖርት፤ የዓለም ዋንጫ ስለተካሄደበት ፤ የብሮድካስት ገቢ በመጨመሩና  ስፖርቱ ለተጨማሪ የገበያ እድሎች ስለተመቸ ነው ብሏል፡፡  
ሪፖርቱን በፊፋ ሚሰራው ትራንስፈር ማቺንግ ሲስተም የተባለው ዲፓርትመንት  ነው፡፡በዓለም አቀፍ ደረጃ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾችን ዝውውር በመከታተል በፊፋ በኩል ሪፖርት ሲያቀርብ አራተኛ ዓመቱ ነው፡፡ መረጃዎቹ ቢያንስ ለሰባት ዓመታት ሲሰባሰቡ ቆይተዋል፡፡ የሚዘጋጅበት ዋና ምክንያት በዓለም የእግር ኳስ ስፖርት ያሉ ባለድርሻ አካላት የስፖርቱን የገበያ ሁኔታ በመረጃ በተደገፈ እውቀት ለመከታተል እንዲያስችል ነው፡፡ አይቲኤምኤስ የተባለው የፊፋ አካል የሆነ ተቋም በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር አባል በሆኑ ሁለት መቶ አገራት ውስጥ ከሚገኙ ስድስት ሺ ክለቦች ጋር በመስራት ድጋፍ ያደርጋል፡፡
በዝውውር ገበያው ብራዚላውያን ተጨዋቾች ከፍተኛውን ብዛት ያስመዘገቡ ሲሆን 646 እዚያው በአገራቸው  689 ደግሞ በመላው ዓለም በመሰራጨት በገበያው ከፍተኛ ተፈላጊ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ብራዚላውያኑ ተጨዋቾች 567 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖባቸዋል፡፡ 801 አርጀንቲናውያን፤ 596 እንግሊዛውያን እንዲሁም 507 ፈረንሳውያን ተጨዋቾች የገበያው አካል ሆነው ተከታታይ ደረጃ ወስደዋል፡፡ በሪፖርቱ እንደተዳሰሰው  የእግር ኳስ ትልቁ ገበያ በሚካሄድባቸው የአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች ላይ 1.35 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ተደርጓል፡፡
የአንድ ተጨዋች አማካይ የዝውውር ሂሳብም ሚሊዮን ዶላር 10.1 ሚሊዮን ተተምኗል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግና በስፔን ላሊጋ የዝውውር ገበያው ተሳትፎ ሲጨምር፤ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ በፊት ያልነበረው ግብይት በከፍተኛ ደረጃ  አድጓል፡፡ በፈረንሳይ ሊግ እና በጣሊያን ሴሪኤ የወጭው መጠን በየዓመቱ ከግማሽ በላይ መቀነሱን ቀጥሏል፡፡
ገበያው በከፍተኛ ሁኔታ የደራባቸው ሁለት አገራት እንግሊዝ እና ስፔን ቢሆኑም እግር ኳስ አትራፊ  በሆነበት አውሮፓ  በገበያው ወጭ 87 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡ በእንግሊዝ ያሉ ክለቦች ከወጪው 67 በመቶ ድርሻ በመውሰድ እስከ 770 ሚሊዮን ዶላር ሲያፈስሱ የስፔን ክለቦች ወጭ ደግሞ እስከ 308 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ዝውውሮችን ያቀላጠፉ ፊፋ የሚያውቃቸው ህጋዊ ኤጀንቶች እና ወኪሎች እስከ 236 ሚሊዮን ዶላር የኮሚሽን ክፍያ አግኝተዋል፡፡
በዓለም እግር ኳስ የዝውውር ገበያ ተፈላጊ የሚሆኑ ተጨዋቾች አማካይ እድሜ 25 ዓመት ከ6 ወር መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት በዓለም እግር ኳስ ገበያ 160 አገራትን በማሳተፍ ከ35ሺ በላይ የተጨዋቾች የዝውውር ተፈፅመዋል፡፡ የአውሮፓና ደቡብ አሜሪካ ተጨዋቾች በከፍተኛ ዋጋቸው  እስከ 20ኛ ያለውን  ደረጃ የተቆጣጠሩ ሲሆን  ከ50 እስከ 119 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በአንፃሩ የአፍሪካዊ ተጨዋች ከፍተኛው ዋጋ ተመን ከ4.5 እስከ 31.8 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የዓለም እግር ኳስ የዝውውር ገበያ የኢትዮጵያዊ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ከፍተኛው  ዋጋ በስዊድኑ ክለብ ቢኬ ሃከን የሚጫወተው የመሃል ተከላካዩ ዋልድ አታ የተተመነበት 601 ሺ ዶላር  ነው፡፡
በፊፋ የተሰራጨው የዓለም እግር ኳስ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ሪፖርት መነሻ ያደረገው የስፖርት አድማስ ዘገባ ሰሞኑን አነጋጋሪ በሆነውና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቀረበውን ረቂቅ ህገ ደንብ በጨረፍታ ይዳስሳል፡፡
ዛሬ ወደ ሩብ ፍፃሜ ከሚሸጋገረው 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ በተያያዘ ደግሞ አፍሪካውያን ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በዓለም እግር ኳስ እየተበደሉ መሆናቸውን ይመለከታል፡፡ አፍሪካውያን በዓለም እግር ኳስ ገበያ የተሰጥኦዋቸውንና የጉልበታቸውን ያህል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ያሳያል፡፡  በፍልሰት፤ በህገወጥ ዝውውርና ዘመናዊ ባርነት ስለመጎዳታቸው  በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ ትንታኔዎች፤ ጥናታዊ ሪፖርቶች እና ዘገባዎችን በመንተራስ  ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያ ገና በተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ረቂቅ ሕገ ደንብ ላይ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በክለቦች ላይ የሚታየውን የተጨዋቾች የዝውውር ስርዓት ወደ ዘመናዊ አሰራር የሚቀይር ያለውን የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ረቂቅ ሕገ ደንብ ከሳምንት በፊት ይፋ አድርጓል፡፡  ፌደሬሽኑ ረቂቅ ህገ ደንቡን አለም የሚከተለውን አሰራር ለመተግበር አዘጋጅቸዋለሁ በማለት ከጥር 25 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሚያደርገው አስታውቋል፡፡ ይሁንና በተለያዩ ሁኔታዎች ረቂቅ ህገ ደንቡ ባለድርሻ አካላትን እያወዛገበ ነው፡፡  በተጨዋቾች ዝውውር ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ያልታወቁ ደላሎችና አጭበርባሪዎችን ለመከላከል እንደሚያግዝ፤ የክለቦች እና የመንግስትን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የተባለው ደንቡ በዘጠኝ ክፍልና በ28 አንቀጽ ተከፋፍሎ ቀርቧል፡፡ እስከ  10 በሚደርሱ አንቀፆች የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በውዝግብ እና በጭቅጭቅ ላይ ናቸው፡፡ የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ረቂቅ ሕገ ደንቡ በዋናነት ብዙ ቅሬታዎችን የፈጠረው የተጨዋቾች ፤ የክለብ ባለቤቶችና አስተዳዳሪዎች ሐሳባቸውን እንዲገልፁበት በቂ እድል አልሰጠም በሚል ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን ረቂቅ ህገ ደንቡን ያዘጋጀው ከኢትዮጵያ ቡና፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ከዳሸን ቢራ፣ ከአርባ ምንጭ ከነማ፣ ከሊግ ኮሚቴ፣ ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎች ባካተተ የጥናት ቡድንን እንደሆነ አስታውቋል፡፡  በደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ የሚተገበረውን ህገ ደንብ ተንተርሶ እንደተዘጋጀ፤  የዓለም አቀፉን እግር ኳስ ማኅበርን ሕግጋት መሠረት እንዳደረገና የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ)፣የተጨዋቾች የዝውውር መርሕን እንደሚከተልም ገልጿል፡፡  ፌደሬሽኑ  በአገሪቱ የሚፈፀመው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር በሕግና በሥርዓት እንዲመራ   ህገ ደንቡ ወሳኝ እንደሆነ ሲያስገነዝብም ፤በፊፋ ዝቅተኛውን የተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር መስፈርት ያሟላ እንዲሆን፣ በተጨማሪም አሠራሩ በሕጋዊ ወኪል እንዲመራና ሒደቱም ተጨዋቾችን፣ ክለቦችንና መንግሥትን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነም አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ የዝውውር ገበያ ካለፈው 4 ዓመት ወዲህ በ50ሺ ብር የፊርማ ክፍያ ተጀምሮ፤ ወደ 100ሺ ብር ከዚያም ወደ 200ሺ ብር፤ 300ሺብር ዋጋዎቹ እያደጉ መጥተው ዘንድሮ ለአንድ ተጨዋች የሚከፈለው የፊርማ ገንዘብ ወይም የዝውውር ሂሳብ በአማካይ እስከ 500ሺ ብር ደርሶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ዳዊት እስጢፋኖስን ለ2 ዓመት ኮንትራቱን እንዲያራዝም የከፈለው 1.2 ሚሊዮን ብር ደግሞ  ሪኮርድ የፊርማ ሂሳብ ነበር፡፡  
የፕሪሚዬር ሊግ ተጨዋቾች ወርሃዊ ደሞዝ በአማካይ 3ሺ ብር  እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡  ዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከመጀመሩ በፊት በተካሄደው የዝውውር ገበያ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ መውጣቱ  ተዘግቦ ነበር፡፡ በወቅቱ አዲስ ተጨዋች  በማስፈረም እና ውሎችን በማደስ 8 ክለቦች ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን ግብይቱ በ73 ተጨዋቾች ላይ የተንቀሳቀሰ ነበር።  መከላከያ እስከ 91 ሚሊዮን ብር፤ ንግድ ባንክ እስከ 62 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ሙገር  እስከ 47 ሚሊዮን ብር ፈሰስ ማድረጋቸው የገበያውን መሟሟቅ የሚያመለክት ነበር፡፡
በሌላ በኩል  ከአምስት እና ስድስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች ከአገር ውጭ የመጫወት እድል ያላቸው በየመን ሊግ ብቻ ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን በግብፅ እና በምስራቅ አውሮፓ እንዲሁም አፍሪካ ውስጥ በሱዳን ፤ በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ ሊጎች በጣት የሚቆጠሩ ተጨዋቾች ዝውውር መፈፀማቸው ይጠቀሳል፡፡ በተያያዘ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለመጫወት ከአፍሪካ 6 አገራት የተውጣጡ ከ26 በላይ ተጨዋቾች በ7 ክለቦች በመቀጠር ለቀጣይ የውድድር ዘመን ህጋዊ እውቅና አግኝተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ  ለመጫወት እውቅና ያገኙት ከሌላ አገር የመጡት ተጨዋቾች ብዛታቸው 26  ይሆናል። 8 ከካሜሮን፤ 7 ከናይጄርያ፤ 6 ከጋና፤ 3 ከኡጋንዳ እንዲሁም ከኬንያ እና ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ናቸው፡፡ ከ26ቱ የሌላ አገር ተጨዋቾች ጊዮርጊስ 7፤ ኤልፓ እና ሀረር ቢራ እያንዳንዳቸው 5፤ ደደቢት 4፤ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከነማ እያንዳንዳቸው 2 እንዲሁም ኒያላ ለ1 ተጨዋች ቅጥር ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡  በፊፋ ህጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው በተጨዋች ወኪልነት የሚሰሩ ባለሙያዎች በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በነበረው አሰራር እንደተጨዋች ወኪል ሆነው  ዝውውርን የሚደልሉት የቀድሞ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች፤ የየክለቡ አሰልጣኞች እና ተፅእኖ አድራጊ ተጨዋቾች፤ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የደጋፊዎች ማህበራት ነበሩ፡፡
በኢትዮጵያ  የነበረው አሠራር  ለክለቦች፣ ተጨዋቾችና መንግሥት ምንም ዓይነት ጥቅም አላስገኘም የሚለው የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ፤ ይልቁንም የክለቦችን የፋይናንስ አቅም ያዳከመ መሆኑንም ይገልፃል፡፡ ተጨዋቾችም በፊርማ ክፍያ እንደወሰዱ ተደርጎ የሚነገረው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የእነሱ እንዳልሆነ፣ በመሐል ለሕገወጥ ደላሎች እንደሚውል፣ በሕገወጥ አሠራር በፕሮፌሽናል ስም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ተጨዋቾች መኖራቸው አንዳንዶቹ የፊርማ ገንዘብ ወስደው እንደጠፉ፣ በፕሮፌሽናል ስም ከሌላ አገር የሚመጡት ብዙዎቹ ተጨዋቾች ችሎታቸው እንደሚያጠያይቅ፣ ተጨዋቾች ከደመወዝ ይልቅ ለፊርማ  ክፍያ እንደሚደራደሩና ተቀብለው ተገቢውን አገልግሎት እንደማይሰጡ፣  ክለቦች  አሳድገው ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም በማሳጣቱ ለታዳጊና ለወጣት ተጨዋቾች  ትኩረት እንዳይሰጡ ማድረጉንም እንደማስረጃዎቹ በዝርዝር አቅርቧል፡፡ በአንድ የውድድር ዓመት ለተጨዋቾች ዝውውር በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ብቻ 140 ሚሊዮን ብር ሲንቀሳቀስ መንግሥት ከገቢ ግብር ሊያገኝ የሚገባውን እስከ 42 ሚሊዮን ብር ማሳጣቱም ተጠቅሷል፡፡
ረቂቅ ህገ ደንቡ በተለያዩ አገሮች የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ሥርዓትን በአስረጂነት እንደተዘጋጀ ቢገለፅም፤ በክለቦችእና በተጨዋቾች በስፋት ትችት እየቀረበበት ነው። የክለቦችና የተጨዋቾች መብቶችን የሚጋፉ አንቀፆች መካተታቸውን በመግለፅ የቀረቡት ቅሬታዎች ይበዛሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹን ደንብና መመሪያዎች በሚወጡበት ወቅት ጉዳዩን ከሕግና መሰል ጉዳዮች ጋር አጣጥመው ማስኬድ የሚችሉ የሕግ ባለሙያዎችን ማካተት ይገባ እንደነበር የተቹም ይገኙበታል፡፡ የኢትዮጵያ ተጨዋቾችን በመወከልም ሃሳብን ለመግለፅ በሚል ለፌደሬሽኑና ለሚዲያ አካላት በተሰራጨው ግልፅ ደብዳቤ ቢያንስ 5 አንቀፆች ላይ የቀረቡ ቅሬታዎች ቀርበዋል፡፡ ዝርዝሩን ሳምንት በስፋት የምንመለስበት ይሆናል፡፡
አፍሪካውያን  በፍልሰት ፤ በዘመናዊ ባርነትና በጉልበት ብዝበዛ ላይ
አፍሪካውያን ፕሮፌሽናል በአውሮፓ ሊጎች 15 በመቶ ውክልና አላቸው፡፡ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከተሳተፉት  368 ተጨዋቾች 248 ያህሉ በ32 የአውሮፓ አገራት  የሚጫወቱ ናቸው፡፡ 75 ከፈረንሳይ፣ 27 ከስፔን፣ 23 ከእንግሊዝ፣ 21 ከቤልጅዬም ሊግ ተገኙ ናቸው፡፡ አፍሪካ ዋንጫው  በ4 አህጉራት፣ በ57 አገራት የሚገኙና 243 ክለቦችን የወከሉ ተጨዋቾች ይሳተፉበታል፡፡   በየአገራቸው የሚጫወቱ  107 ሲሆኑ በ17 አገራት ያሉ 58 ክለቦችን የወከሉ ናቸው፡፡ አፍሪካውያን በመላው ዓለምም ተሰራጭተዋል፡፡ ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች አገራት ባሻገር በምስራቅ አውሮፓ፤ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሩቅ ምስራቅ ኤስያም አርሜንያ፤አንዶራ፤ጂብራላተር እና ኢስቶንያ፤  ሆንግ ኮንግ፤ በቻይና፤ ህንድ፤ ባንግላዴሽ እና በኢራን፤ በሰሜን አሜሪካ ሜክሲኮ ውስጥ በሚገኙ የሊግ ውድድሮች አፍሪካዊ ፕሮፌሽናል ተጨዋች አይታጣም፡፡
አፍሪካውያን አህጉራቸውን በመልቀቅ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰራጩበት ምክንያት በስፖርቱ በተሻለ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆን አንፃር ነው። የሚገባቸውን ያህል ባያገኙበትም በተፈጥሯዊ ብቃታቸውና ተሰጥኦቸው አፍሪካውያን ተፈላጊ ናቸው። አፍሪካ ውስጥ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን በደህና ደሞዝ በመቅጠር የሚያጫወቱ አገራት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።   በግብፅ፤ በደቡብ አፍሪካ፤ በአንጎላ፤ በዲሪ ኮንጎ ያሉ ክለቦች ብቻ በዝቅተኛ ደረጃ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ፍልሰት የመገደብ አቅም ያዳበሩ ናቸው። ይሁንና በእነዚህ አገራት ያሉ ክለቦች ወርሃዊ ደሞዝ ቢከፍሉ ዝቅተኛው 150 ከፍተኛው 600 ዶላር ነው፡፡ በአውሮፓ ሳይሆን ለምሳሌ ያህል በባንግላዲሽ ለአንድ አፍሪካዊ ተጨዋች እስከ 2000 ዶላር ወርሃዊ ደሞዝ ይታሰባል፡፡ ስለሆነም የአህጉሪቱ ክለቦች የፋይናንስ አቅም ተወዳዳሪ አለመሆንና  በፕሮፌሽናል ደረጃ ያን ያህል አለማደጋቸውም ተፅእኖ ፈጥሮ ፍለሰቱን እንዳባባሰውም ይገለፃል፡፡
ከወር በፊት በታዋቂው የእንግሊዝ ታብሎይድ ዴይሊሜል በተሰራጨው ዘገባ በመላው ዓለም በ34 አገራት ያሉ ሊጎች የደሞዝ ሁኔታ ተዳስሶ ነበር፡፡ የአንድ ፕሮፌሽናል ተጨዋችን አማካይ ደሞዝ በማስላት ደረጃ ለማውጣት ነበር፡፡ በከፍተኛ ደሞዝ ከፋይነት የመጀመርያውን ደረጃ የወሰደው ለአንድ ፕሮፌሽናል ተጨዋች 66.4ሺ ዶላር በሳምንት የሚከፍለው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሲሆን፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 42.2 ሺ፤ የጣሊያን ሴሪኤ 38 ሺ፤ የስፔን ላሊጋ 35.3 ሺ እንዲሁም የፈረንሳይ ሊግ 1 28.5 ሺ ዶላር ሳምንታዊ ደሞዝ በመክፈል እስከ አምስት ያለውን ደረጃ አከታትለው ወስደዋል፡፡
በዴይሊ ሜል ጥናታዊ ዘገባ መሰረት አፍሪካ ውስጥ የሚካሄዱ የሊግ ውድድሮች ለተጨዋቾች በሚከፍሉት ደሞዝ በደቡብና ሰሜን አሜሪካ አህጉራት፤ ከኤስያ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከምስራቅ አውሮፓ አገራት የሊግ ውድድሮች እጅግ ዝቅ ያሉ ናቸው፡፡ በደረጃ ውስጥ ለመግባት የቻሉትም በሁለት የአፍሪካ አገራት የሚካሄዱ ሊጎች ናቸው፡፡ በአልጄርያ የሚካሄደው የሊግ ውድድር ለአንድ ፕሮፌሽናል ተጨዋች በሳምንት 2005 ሺ ዶላር አማካይ ሳምንታዊ ደሞዝ በመክፈል 28ኛ ደረጃ ሲያገኝ ለናይጄርያ ሊግ ደግሞ 196 ዶላር አማካይ ሳምንታዊ ደሞዝ እየተከፈለ 31ኛ ደረጃ ተሰጥቷል፡፡
አፍሪካውያን በእግር ኳስ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች መፍለሳቸው የአህጉሪቱን እግር ኳስ ከማዳከሙም በላይ አስከፊ እየሆነ የመጣው ይህ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ህልማቸው ለዘመናዊ  ባርነት አጋልጧቸው መጎሳቆላቸው ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በ20ሺዎች የሚገመቱ አፍሪካውያን በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋችነት ህልም ተታትለው ወደ አውሮፓ በመሰደድ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሆነዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር እና በየአህጉሩ ያሉት የእግር ኳስ ተቋማት እድሚያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑትን በእግር ኳስ ምክንያት ማዘዋወር የሚከለክል ህግ ቢኖራቸውም ተግባራዊነቱ ደካማ መሆኑ በእግር ኳስ ዘመናዊ ባርነት መኖሩን አጋልጦታል፡፡ አፍሪካውያን ታዳጊዎች  በየአገሮቻቸው ባሉ አካዳሚዎች በ12 እና 13 ዓመት እድሜያቸው በቂ ስልጠና እና ትምህርት ሳያገኙ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ህልም ወደ አውሮፓ እየተላኩ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታም በተለይ በምእራብ አፍሪካ የሚገኙ አካዳሚዎች በአሳሳቢ ሁኔታ ተስፋፍቶ ይስተዋላል፡፡ አካዳሚዎቹ ታዳጊዎችን 70 በመቶ በማሰልጠን ለፕሮፌሽናል ደረጃ አብቅተው በማሰልጠን 30 በመቶውን በአውሮፓ እግር ኳስ እንዲያሳድጉ ማድረግ ነበረባቸው፡፡
በተገላቢጦሽ የሚከተሉት አሰራር ግን የበርካታ አፍሪካውያን ወጣቶች ህልምን በአጭሩ እያስቀረ ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ አፍሪካውያን እግር ኳስ ተጨዋቾች በየአገራቸው ካሉ አካዳሚዎች በወጣትነታቸው ወደ አውሮፓ እና የተለያዩ ዓለም ክፍሎች በመሰደድ ላይ ናቸው፡፡ በተለያዩ ህገወጥ የዝውውር ደላሎች ተታልለው መፍለሳቸው የሚመኙትን የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተመክሮ እንዳያሳኩ ሆነዋል፡፡
በማይረባ ክፍያ እና ጥቅም ጉልበታቸው እየተበዘበዘም ነው፡፡ በእድሜያቸው ገና የሆኑ አፍሪካውያን ታዳጊዎችም በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ህልም ለጉልበት ብዝበዛ፤ ለከፋ ድህነት እና ጉስቁልና እየተዳረጉ ናቸው። እድሜያቸው ከ13 በታች የሚሆናቸውን አፍሪካውያን በህገወጥ ፍልሰት የሚያሰቃዩ ሃሰተኛ የተጨዋቾች የዝውውር ደላሎች በዝተዋል፡፡ የፈጠሩት ስግብግብ የንግድ መረብን ለመቆጣጠር የሚያዳግትበት ደረጃም ተደርሷል፡፡ በምእራብ አፍሪካ ውስጥ ህገወጥ እና ሀሰተኛ የእግር ኳስ ዝውውር ደላሎች ብቻ ሳይሆኑ ፍቃድ የሌላቸው አካዳሚዎች በሺዎች ሆነው መንቀሳቀሳቸው ችግሮቹን አባብሷቸዋል፡፡
ለታዳጊ ተጨዋች ቤተሰቦች የአውሮፓ እግር ኳስን የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ህልም ቃል በመግባት እና እስከ 10ሺ ፓውንድ በማስከፈል ህገወጥ ዝውውር የሚያደርጉ ህገወጥደላሎች መኖራቸውም ይጠቀሳል። በተለያዩ ጊዜያት ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ አስተዳደር ተቋማት፤ የስፖርት ባለሙያዎች እና ምሁራን እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ በአፍሪካውያን የእግር ኳስ ባርነት በተለይ በምእራብ አፍሪካ አካዳሚዎች የተበላሸ አሰራር እና ህገወጥ የተጨዋቾች ዝውውር አጀንዳዎች ዙርያ የተቃውሞ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ የፊፋው ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችን በዓለም የእግር ኳስ ገበያ ላይ ማሳተፍን የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ የባርያ ንግድ ብለው በተደጋጋሚ ያወገዙት ሲሆን፤ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሚሸል ፕላቲኒ በበኩሉ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ የከፋ ደረጃ በሚል ተቃውሞውን ገልጿል፡፡ በዓለም እግር ኳስ የአፍሪካዊ ተጨዋች ዋጋም ከሚኖረው አስተዋፅኦ ጋር ከሌላው ዓለም በንፅፅር ሲታይ ዝቅተኛ ነው፡፡ በአፍሪካዊ ተጨዋች አዲስ የዝውውር ሂሳብ ሪከርድ በዓለም እግር ኳስ የተመዘገበው ባለፈው ሰሞን ነው፡፡ የ26 ዓመቱ ኮትዲቯራዊ ዊልፍሬድ ቦኔ ከእንግሊዙ ክለብ ስዋንሲ ሲቲ  ወደ ማንችስተር ሲቲ የተዛወረበት 422 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ዊልፍሬድ ቦኔ ባለፉት አምስት ዓመታት የአውሮፓን እግር ኳስ ትኩረት ስቦ የቆየ ተጨዋች ነበር፡፡ በአፍሪካ ኮከብ ተጨዋችነት ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በካፍ ለመሸለም የበቃው ያያ ቱሬ እና ኤጀንቱ ዲምትሪ ሲሊክ የአፍሪካውያን ችሎታ እና አስተዋፅኦ በአውሮፓ እግር ኳስ ያን ያህል የሚገባውን ዋጋ እያገኘ እንዳልሆነ እና ክብር እንደማይሰጣቸው በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ተሰምተዋል፡፡
ሴኔጋላዊው ዴምባ ባ በአፍሪካውያን ተጨዋቾች ላይ በዓለም እግር ኳስ ገበያ ላይ ያለውን ዝቅተኛ ዋጋ አሰጣጣጥ ለማሳየት ሂሳብ ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡ ባ በሶስቱ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ዌስትሃም፤ ኒውካስትል እና ቼልሲ ስኬታማ የውድድርዘመናትን በማሳለፍ ካገኘው ከፍተኛ ልምድ በኋላ አምና ወደ ቱርኩ ክለብ ቤሲክታስ የተዛወረው አስቀድሞ ከነበረው የዋጋ ግምት 100 ፐርሰንት ርካሽ ሂሳብ ቀርቦለት በ7.1 ሚሊዮን ፓውንድ ብቻ ነበር፡፡ ለአፍሪካውያን ተጨዋቾች በዝውውር የሚወጣው ሂሳብ ከላቲን እና ከአውሮፓ ተጨዋች አላግባብ ያነሰ እንደሆነም ተንታኞች ይገልፃሉ። አፍሪካውያን ተጨዋቾች ወደ አውሮፓ ክለቦች ሲዘዋወሩ የሚገባቸውን ክፍያ ከማግኘት ይልቅ በወረደ ሂሳብ እንዲፈርሙ ይገደዳሉ፡፡ አላግባብ ጉልበታቸው ይበዘበዛል፡፡ በየክለቦቹ ጉልበት እና ሃይል ሰጪ ሆነው ብቻ ይታያሉ፡፡ ከእነ ሳሙኤል ኤቶ፤ ከዲድዬር ድሮግባ እና ከእነኤስዬን በኋላ በመላው አውሮፓ በሚገኙ ትልልቅ ክለቦች በመዘዋወር በከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ እና ደሞዝ የሚቆጠር አፍሪካዊ ተጨዋች ከያያ ቱሬ በኋላ እንደማይኖር ይገለፃል፡፡
በስዊዘርላንድ ተቀማጭ የሆነው ሴንተር ፎር ስፖርት ስቲዲስ በ2014 እኤአ የዓለማችን 120 ውድ ተካፋይ ተጨዋቾች ዝርዝር ሠርቶ ነበር ፡፡ ዓለም አቀፉ ተቋም ዝርዝሩን ለማጠናቀር ከ2009 ጀምሮ እስከ 2014 የተፈፀሙ ከ1500 በላይ ዝውውሮችን ዳስሷል። በዚሁ ዝርዝር 4 አፍሪካውያን ብቻ መካተታቸው ተስተውሏል፡፡ በዓለም እግር ኳስ ምን ያህል እየተጎዱ እንደሆነና በዝውውር ገበያው በርካሽ እየተነገደባቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ የአራቱ አፍሪካውያን አጠቃላይ የዝውውር ሂሳብ ከ136 ሚሊዮን ዶላር በታች ነው፡፡ 45ኛ ላይ የሚገኘው ለማንችስተር ሲቲ የሚጫወተው ኮትዲቯሯዊው ያያ ቱሬ ለዝውውር በወጣበት 37.7 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ሌሎቹ ሁለት ኮትዲቯራዊያን ተጨዋቾች በጣልያኑ ኤስ ሮማ የሚገኘው ጀርቪንሆ እና በስዋንሴ ሲጫወት በ27.1 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ የነበረው ዊልፍሬድ ቦኒ ናቸው፡፡ አራተኛው ተጨዋች በጀርመኑ ባየር ሙኒክ የሚገኘው አልጄርያዊው መሃዲ ቤናት ለዝውውር በተከፈለበት 22.6 ሚሊዮን ዶላር በ87ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
አፍሪካውያን ተጨዋቾች በዓለም የእግር ኳስ በባርነት ከመጎሳቆላቸው፤ አነስተኛ ደሞዝ ተከፋይ ከመሆናቸው ባሻገር ከሜዳ ውጭ በሚያገኙት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችም የተበደሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ኮትዲቯራዊውን ያያ ቱሬ  በሱ ደረጃ ካሉ ትልልቅ ፕሮፌሽናሎች በማስታወቂያ እና በስፖንሰርሺፕ ውሎች ዓመታዊ ገቢው ብናነፃፅር ገቢው በአምስት እጥፍ እንደሚበልጥ እንረዳለን፡፡ እነ ቱሬ በማስታወቂያ እና በስፖንሰርሺፕ ውሎች በዓመት በአማካይ እስከ 4.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲኖራቸው ብዙዎቹ የአውሮፓ ተጨዋቾች ግን በአማካይ ከ15.1 ሚሊዮን ዶላር በላይ  የሚያገኙ ናቸው፡፡

  • የሰለጠነ ተቃዋሚ በላቀ ብስለት እንጂ በእልህ አይመራም
  • የአስለቃሽ ጭስ ችግራችንን ኒዮሊበራል መንግስታት ይታደጉን  
  • እነ “አንድነት” እርስ በርስ ከሚወነጃጀሉ ቢናዘዙ ይሻላቸው ነበር

     እንዳለፉት ሳምንታት ሁሉ የዛሬውም ጉዳያችን ትንሽ ጠነን የሚል ስለሆነ፣ ወጋችንን ዘና ብለን እንጀምረው - በቀልድ፡፡ መጀመሪያ “ቀልድታትን አሽሙራትን ምህረይ ወሊሃንስ” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ ከወጣ የትግርኛ መጽሐፍ ውስጥ እኔና ጓደኞቼን በሳቅ ካፈረሱን ቀልዶች (ስላቆች) መካከል አንዱን ላቅምሳችሁ፡፡ በነገራችን ላይ የመፅሐፉ ዳሰሳ (Review) በጥበብ አምድ ላይ ስለወጣ አብዛኛውን ጉዳይ ከዚያ ልታነቡ ትችላላችሁ፡፡
የመፅሐፉ ባለታሪክ ምህረይ ወልደዮሐንስ፤ በአክሱም “እብድ” እየተባሉ የኖሩና እሳቸውም ማበዳቸውን ተቀብለው እስከ ዕለተ ሞታቸው የኖሩ ታላቅ ሰው እንደነበሩ አዘጋጁ ጠቁሟል፡፡ እናላችሁ…ምህረይ አንዱን ታጋይ እንዲህ ይሉታል፤ “ደርግ ስኳር ይሰጠን ነበር፤ ጡረታም ይከፍለናል፤ እናንተ ይሄን ሁሉ ጊዜ ታግላችሁ…ለህዝቡ ምን ይዛችሁ ነው የመጣችሁት?”
ታጋዩም፤ “ዲሞክራሲ” ሲል ይመልሳቸዋል፡፡
“ዲሞክራሲ ደሞ ምንድነው?” ይጠይቁታል
“ሰው ሃሳቡን እንደፈለገ ያለገደብ በነፃነት የሚናገርበት መብት ነው” ሲል ያስረዳቸዋል፡፡
ምህረይም፤ “እህ… እንዲህ እንደኛ” ይሉታል (እንደ አበድነው ማለታቸው ነው)
አንድ ሌላ ቀልድ ደግሞ ልመርቅላችሁ - ከባህርማዶ፡  
አንድ ራሽያዊ ከአገሩ ይሰደድና ሰተት ብሎ አሜሪካ ኒውዮርክ ሲቲ ይገባል፡፡ በከተማዋ ጐዳና ላይ ሲዟዟር ይቆይና ፊትለፊት ያገኘውን የመጀመሪያ ሰው በማስቆም፤ “ሚ/ር አሜሪካ፤ ወደ አገራችሁ እንድገባ ስለፈቀዳችሁልኝ አመሰግናለሁ፡፡ ምግብ፣ መኖሪያ ቤት፣ ህክምና፣ ትምህርት…በነፃ ስለሰጣችሁኝ ልባዊ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ!” ይለዋል - ከልቡ፡፡
ስደተኛውን ሲያዳምጥ የቆየው መንገደኛም፤ “ተሳስተሃል የእኔ ወንድም፤ እኔ አሜሪካዊ አይደለሁም፤ የሜክሲኮ ተወላጅ ነኝ” በማለት ይመልስለታል፡፡
ስደተኛው ትንሽ እንደተጓዘ ሌላ ሰው ያገኝና፤ “እንዲህ ያለች ውብ አገር ስለፈጠራችሁ አመሰግናለሁ”  
ሰውየውም፤ “እኔ አሜሪካዊ አይደለሁም፤ ቬትናም ነኝ” ሲል ይመልስለታል፡፡
ራሽያዊ ስደተኛው ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ጥቂት እንደተጓዘ መንገድ ላይ የገጠመውን አንድ ሰው ያስቆምና ከጨበጠው በኋላ፤ “ድንቅ አድርጋችሁ ለፈጠራችኋት አሜሪካ አመሰግናለሁ” በማለት ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
ሰውየው ግን፤ “እኔ የመካከለኛው ምስራቅ ሰው እንጂ አሜሪካዊ አይደለሁም” ብሎት ጥሎት ይሄዳል፡፡ ግራ የተጋባው ስደተኛ በመጨረሻ አንዲት ሴት ያገኛል፡፡ “አሜሪካዊት ነሽ የእኔ እመቤት?” ይጠይቃታል፡፡
ሴትየዋም፤ “አይደለሁም፤ አፍሪካዊት ነኝ” ትለዋለች።
ስደተኛው ሴትየዋን አፍጥጦ እየተመለከታት፤ “ታዲያ አሜሪካኖቹ የት ነው ያሉት?” ብሎ ይጠይቃታል፡፡
አፍሪካዊቷ ሴት ሰዓቷን አየት ታደርግና፤ “ሥራ ላይ ሳይሆኑ አይቀሩም” ትለዋለች፡፡
በእርግጥም ሥራ ላይ መሆን አለባቸው፡፡ ያለዚያማ ከመላው ዓለም ለሚጐርፍ ስደተኛ የሚበቃ አገር መፍጠር አይችሉም ነበር፡፡ ያውም የታተረ ሁሉ የሚበለፅግባት፤ ሞልቶ የተረፋት ዕፁብ ድንቅ የዲሞክራሲ አገር!! አያችሁ ልዩነታችንን?! እኛ እኮ በፖለቲካው በሉት በኢኮኖሚው አገራችን ለራሳችን እንኳን ስላልበቃችን (አንሳ ሳይሆን በመልካም አስተዳደር ችግር!) ዓይንና ልባችን ስደትን እያማተረ ነው፡፡ (“ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” አሉ!)
ሰሞኑን ምሽት ላይ ብቸኛ የማታ መተከዢያዬ (መዝናኛዬ ብላችሁ ዋሾ እሆንባችኋለሁ!) የሆነውን EBCን ስመለከት፤ፕሮግራሙ የአፋርና የሶማሊያ አርብቶአደሮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ እናም ከጉዳዩ ባለቤት (From the horse’s mouth!) እንዲህ የሚል አስተያየት ሰማሁ፤ “የሶማሊያ አርብቶ አደር ችግር:- አንደኛ - ውሃ። ሁለተኛ - ውሃ፡፡ ሦስተኛ - ውሃ፡፡” (ትልቁ ችግራቸው የውሃ እጦት እንደሆነ አስረግጦ መናገሩ ነው!) “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” እንደሚባለው…እኔ ደግሞ ወዲያው በፖለቲካ መነዘርኩት፡፡ እናም የጦቢያ ፖለቲካ ችግር “አንደኛ - አለመደማመጥ፡፡ ሁለተኛ - አለመደማመጥ። ሦስተኛ - አለመደማመጥ፡፡” ስል አሰብኩ፡፡ ከምሬ እኮ ነው…ዋና ችግራችን እኮ ሌላ ሳይሆን አለመደማመጥ ነው፡፡ በቃ ፈርዶብን አንደማመጥም፡፡ ተቃዋሚዎች እርስ በርስ አይደማመጡም፡፡ ተቃዋሚዎችና ኢህአዴግ ፈጽሞ አይደማመጡም፡፡(“አንዱ ሲናገር ሌላው ጆሮውን ይደፍናል!”) ተቃዋሚዎችና ምርጫ ቦርድ አይደማመጡም፡፡ ኢህአዴግና ህዝቡ (ህዝብ እኛ ነን!) አንደማመጥም፡፡(መሰረቱ ህዝብ መሆኑን ብናውቅም!) ተቃዋሚዎችና የመንግስት ተቋማት አይደማመጡም፡፡
ያለመደማመጥ --- ውጤቱ ደግሞ ያለመግባባት፣ ባስ ሲልም ቀውስ ነው፡፡ ያውም ዘርፈ ብዙ ቀውስ… የፖለቲካ ቀውስ -- የኢኮኖሚ ቀውስ… ማህበራዊ ቀውስ -- አገራዊ ቀውስ!!! እኔ የምላችሁ ግን … በአንድ ቋንቋ እያወራን ለምንድነው የማንደማመጠው? አደራ! መልሱን ከእኔ እንዳትጠብቁ! (ለሀገር ሙሉ ችግር እንዴት መልስ አገኛለሁ!) ላለመደማመጣችን ማስረጃ ትፈልጋላችሁ እንዴ? (ሞልቶ ተርፎናል!) አሁን ለምሳሌ ኢህአዴግ የምርጫ ስነምግባር ኮዱን ካልፈረሙ ፓርቲዎች ጋር ጠበል ፃዲቅ አልጠጣም ብሎ ምሎ ከተገዘተ ስንት ዓመቱ ነው? ተቃዋሚዎችም ከድርድር በፊት አንፈርማትም ብለው እልህ ከገቡ ስንት በጋ ጠባ? ሆኖም ግን ዘንድሮም እንደ አዲስ ተነስቷል፡፡ ለምን? አይደማመጡማ! ቢደማመጡማ… ሌላ የመግባቢያ ሃሳብ ያፈልቁ ነበር - ቢያንስ ከሁለት አንዳቸው፡፡(ግን እኮ ለመደማመጥም ሌላውን ማክበር  ይጠይቃል !) እኛ ደግሞ ከራሳችን ውጭ ሌላውን ማክበር ውርደት ይመስለናል፡፡ (ነቄ አይደለንማ!)
እኔ የምላችሁ…በምርጫ መዳረሻ ላይ ዕጣፈንታቸው መከፋፈልና መሰነጣጠቅ የሆኑት መኢአድና አንድነት እንዴት እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ እንደሰነበቱ አያችሁልኝ አይደል?! (“ትዝብት ነው ትርፉ” አለ ሀበሻ!) አሁንማ ቦርዱ ገላገለን! በነገራችን ላይ…የተከፈሉት የሁለቱ ፓርቲዎች ቡድኖች ሲሰነዝሩት ለነበረው ውንጀላ ሁሉ ተጠያቂ መሆናቸውን የሚያጡት አይመስለኝም። (ፓርቲው ውስጥ ነበሩ ብዬ እኮ ነው!) እናላችሁ…ቢያንስ እነ እገሌ ፈፀሙት ብለው ከሚካሰሱ፣እንደ ኑዛዜ ቢያቀርቡልን የተሻለ ነበር፡፡ (እግረመንገዳቸውንም ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቃሉ ብዬ እኮ ነው!) እርግጠኛ ነኝ… በመሰንጠቃቸው ወይም በመከፈላቸው ብቻ አንዱ ወገን ከደሙ ንፁህ እሆናለሁ ብሎ የሚያስብ አይመስለኝም (እንዴት ይሆናል? በ11ኛው ሰዓት!)
እኔ የምለው ግን … ከዳያስፖራ የሚመጣ ገንዘብ በግል አካውንት ሲገባ፣ አመራሮች ሲበለፅጉበት፣ ፓርቲዎቹ ሲመዘበሩ፣ ሥርዓተ አልበኝነት ሲሰፍን፣ አምባገነንነት ሲንሰራፋ፣ ዳያስፖራው ያልተገባ ተፅዕኖ ሲያሳድር፣ ግለሰቦች ፓርቲዎቹን የግል ኩባንያ ሲያደርጉ፣ ወዘተ… (በኢቢሲ የሰማሁትን ነው!) በማለት ሲወነጅሉ የሰነበቱት ቡድኖች የማንን ጎፈሬ ሲያበጥሩ ነበር? (ከሆነ አይቀር ሃቅ ሃቁን ነዋ!) አብረው ሲያፀድቁ፣ አብረው ሲመርጡ፣ አብረው ሲጥሉ፣ አብረው ሲክቡ፣ አብረው ሲያፈርሱ፣ አብረው ሲመክሩ…አልነበረም? (መቼም ትግላቸው ህቡእ አልነበረም!)
 በነገራችን ላይ ይሄ የፓርቲዎች ክፍፍል በአንዳንድ ፓርቲዎቹን ለማዳከም ባለሙ ኃይሎች ሆን ተብሎ የተፈጠረ ነው ቢባልም ለእኔ ግን ተጠያቂዎቹ ባለቤቶቹ ናቸው - ራሳቸው ፓርቲዎቹ!! የውስጥ ችግራቸውን ወይም ክፍተታቸውን ቀድመው ቢፈቱ ወይም ቢደፍኑ ኖሮ ይሄ ሁሉ ምስቅልቅል ባልተፈጠረ ነበር፡፡ (ያውም ለህዝብ በሚያጋልጥ ሰዓት!) እሺ ችግሩስ ይፈጠር…(ፓርቲዎች የመላዕክት ስብስብ አይደሉምና!) ግና በሆነ መንገድ ተማክረው እንዴት መግባባት ላይ መድረስ አቃታቸው? (የዜሮ ፖለቲካል ጌም ጣጣ እኮ  ነው!) ምርጫ ቦርድ እንዳለው፤ ቢያንስ ለሚደግፋቸው ህዝብ ብለው ሊስማሙ ይገባ ነበር፡፡ (መደማመጥ ከየት ይምጣ!)
 ይኸውላችሁ ባለፈው ሳምንት እንዳወጋነው…እርስ በእርስ መጠላለፍ፤ መወነጃጀልና መናቆር የኋላቀር ፖለቲካ ዓይነተኛ ምልክት ነው፡፡ (መደማመጥም እንደ ዲሞክራሲ ሂደት ነው እንዳትሉኝና እንዳልስቅ!) እንግዲህ የኋላቀር ፖለቲካችን ማሳያዎች የትየለሌ---አይደሉ?! የሰሞኑን የሰላማዊ ሰልፍ ጉዳይና ያስከተለውን ቀውስ እንመልከት፡፡ በነገራችን ላይ በጦቢያችን ብዙ አገራዊ መግባባት (Consensus) ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ቆይ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ፈቃድ ነው ዕውቅና የሚያስፈልገው? ይሄን ጉዳይ የሚመለከተው መንግስታዊ አካል ሥልጣኑ እምን ድረስ ነው? ሰላማዊ ሰልፍ ወንጀል የሚሆነው መቼ ነው? ወንጀል ሲሆንስ…ቅጣቱ ምንድነው? እዚህ ጋ ህግና ህገመንግስቱን አልጠቅስም፡፡ (ሁለቱም ወገኖች ህገመንግስቱ መጣሱን እየተናገሩ ነዋ!) በሱ ብንመራማ (ብንደማመጥ እንደማለት ነው!) የእሁዱ ቀውስና በየጊዜው የሚነሳው ውዝግብ ባልተከሰተ ነበር፡፡ በማንም ላይ እየፈረድኩ እንዳልሆነ ዕወቁልኝ! (መፍረዴማ አይቀርም!)
አያችሁ … ለመፍረድ እየቸኮልን እኮ ነው መደማመጥ ያቃተን፡፡ ባለፈው እሁድ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ዕውቅና ሳያገኙ ሰልፍ ወጡ የተባሉ የአንድነት ፓርቲ አመራሮችና አባላት በጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው የቆሰለ ገላቸውን እያሳዩ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡ እኔ የምለው--- በ21ኛው ክ/ዘመን የምን ዱላ ነው? የምንስ ድብደባ? በሰለጠነ መንገድ ቁጭ ብሎ መወያየቱ ባይሆንልን እንኳን… እንዴት ራሳችንን ከዱላ ማቀብ ያቅተናል? ህግ የጣሱትን በህጋዊ አሰራር ለፍርድ ማቅረብ አይቻልም ነበር? (ኧረ እንደማመጥ!)
እኔ የምለው ግን … ፖሊስ የመደብደብ ፈቃዱ እምን ድረስ ነው? (ለመረጃና ለጠቅላላ ዕውቀት ብዬ ነው!) በነገራችን ላይ ፈቃድ አለው ከተባለም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዎርክሾፕ ቢጤ መካሄድ ያለበት ይመስለኛል፡፡ (ለፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን ለዜጐችም ጭምር!) መብትና ግዴታችንን እንድናውቅ እኮ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም በዕለቱ የአንድነት ሰልፈኞች በፀጥታ ሃይሎች ላይ ድብደባ መፈፀማቸውን ጠቁሞ፤ “የወሰድኩት ራስን የመከላከል ተመጣጣኝ እርምጃ ነው” ብሏል፡፡ አሁንም ለመፍረድ አትቸኩሉ፡፡ ግራ ቀኙን ሳይመዝኑ መፍረድ ነው እቺን ምስኪን አገራችንን ለጥላቻና ለፅንፈኛ ፖለቲካ የዳረጋት። (“ተመጣጣኝ እርምጃ” ሌላ አገራዊ መግባባት ያልተደረሰበት ጉዳይ ይመስለኛል!)
አንድ ሁነኛ ጥያቄ አለን - ለልማታዊ መንግስታችን፡፡ በ97 የነበረው የአስለቃሽ ጭስ ችግር አሁንም አልተፈታም እንዴ? ቀላል እኮ ነው… እነ እንግሊዝን እንዲታደጉን መጠየቅ ነው (ኒዮሊበራል ቢሆኑም የአስለቃሽ ጭስ ድጋፍ ቢያደርጉልን ችግር የለውም!) ከምሬ እኮ ነው… በምዕራብ አገራት የሚገኙ ቀንደኛ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፣የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ እያሉ በየዓመቱ ሪፖርት ለማውጣት ከሚጣደፉ ቢያንስ በቂ የአስለቃሽ ጭስ ድጋፍ ሊያደርጉልን ይገባል፡፡ አስለቃስ ጭሽ እኮ የ21ኛው ክ/ዘመን የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች አክሰሰሪ ነው፡፡ (“Prevention is better than cure” የጤና ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ መብትም መርህ ነው!)
ይሄን ሁሉ የተንደረደርነው ወደ አንድ መቋጫ ለማምራት ነው፡፡ አዎ---ህግ መጣስም ሆነ የ“ድብደባ” እርምጃ የሥልጣኔ ምልክት አይደለም፡፡ (ዓላማችን ዲሞክራሲን ማጐልበትና የሰለጠነ ህዝብ መፍጠር ከሆነ ማለቴ ነው!) መቼም ኢህአዴግም ቢሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ “ተቃዋሚዎችን የሚደበድብ መንግስት” የሚል ስም እንዲወጣለት የሚፈልግ አይመስለኝም (አስለቃሽ ጭስ አልቆበት እንጂ!) ይሄ ነገር እኮ የአገርንም መልካም ገጽታ ክፉኛ ይጎዳል (ቶሎ የማይለቅ ጥላሸት ነው የሚቀባው!) እናላችሁ…በ21ኛው ክ/ዘመን ተቃዋሚን መደብደብ አይመከርም። (ከእነ አምነስቲ ግን ይሄን ትሁትነት እንዳትጠብቁ!)
እግረ መንገዴን (ከዋናው ጉዳይ የወጣ ቢሆንም!) ለኢህአዴግ አንድ ምክር ጣል አድርጌ ልለፍ፡፡  (ቢያዳምጠኝም ባያዳምጠኝም!) እርግጠኛ ነኝ ዛሬም ባይሆን ሌላ ጊዜ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ (ቆይቶ ነው የሚባንነው ሲባል ሰምቻለሁ!) ምክሩ ምን መሰላችሁ? የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ የሆኑትን እነ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ)፣ ፍሪደም ሃውስ ወዘተ… የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን የሚመለከት ነው። ኢህአዴግ እነዚህንና አጋሮቻቸውን የቱን ያህል እንደሚጠላቸው በየጊዜው ከሚያወጣቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል፡፡ (ስሙን “ጥላሸት እየቀቡበት”  እንዴት አይጠላቸው?!) ነገር ግን ተቋማቱን መጥላትና ማጥላላት ብቻውን ያመጣው ለውጥ እንደሌለ ለዓመታት አይተነዋል። (በየዓመቱ አሉታዊ ሪፖርት ከማውጣት አልተገቱማ!) እናም… መፍትሄው ማጥላላትና መጥላት ሳይሆን ተመሳሳይ አገር በቀል ተቋማትን ማብዛትና ማጠናከር ብቻ ነው፡፡ (“የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ” እንዲሉ!) አንዳንዶች እንደሚሉት ወይም እንደሚሰጉት፣ የይምሰልና ተለጣፊ ከሆኑ ግን  ምንም ፋይዳ የለውም። አገር በቀል ተቋማቱ ሙሉ በሙሉ ነፃና ገለልተኛ ሆነው በአገሪቱ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሃቅና በድፍረት የሚያጋልጡ ሊሆኑ ይገባል፡፡
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ኢህአዴግ ጥርሱን ነክሶ መጨከን ያለበት፡፡ (ፈታኝ ቢሆንም የማይቻል ግን አይደለም!) በዚያ ላይ እነ አምነስቲ .. ስሙን ከሚያጠፉት ገለልተኛ አገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተቋማት እንዲፈጠሩ ዕድል መስጠት የተሻለ አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ለፕሬስና ለጋዜጠኛ መብትና ነፃነት የሚቆሙ ገለልተኛ ማህበራትና ተቋማትም እንዲሁ እንዲመሰረቱና እንዲጎለብቱ እድል መስጠት ከኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞች ተፅዕኖ ነፃ መውጫ ብቸኛ መንገድ ይመስለኛል፡፡ (አሁን “ያሉትስ?” እንዳትሉኝና እንዳልስቅ!)
ከምሬ ነው የምላችሁ … ይሄን ምክሬን ኢህአዴግ ዘግይቶም ቢሆን ከተገበረው ከማንም በላይ የሚጠቀመው ራሱ ነው! “ዲሞክራሲ ለእኛ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” ለሚል ፓርቲም ሆነ መንግስት ይሄን እውን ማድረግ ሊያስቸግረው አይገባም፡፡ እርግጥ ነው በአንድ ቀን ጀንበር የሚሆን አይደለም - ሂደት ነው፡፡ ግን ደግሞ ሂደቱ ዛሬ መጀመር አለበት፡፡ ከሁሉም የሚቀድመው ታዲያ መደማመጥ መሆኑን ሳንረሳ ነው! በተረፈ ምርጫውን ከልባችን ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እናድርገው፡፡ (በነቢብም ሆነ በገቢር!)
የፖለቲካ ወጌን የምቋጨው ከሰሞኑ የኢቢሲ “አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች” መካከል ቆፍጠን ያሉ ባልቴት ሴትዮ የሰጡትን አስተያየት በመጥቀስ ነው። “ሰማያዊ ምናምን ትላላችሁ--- እኔ ግን በደንብ አውቃቸዋለሁ---ሁሉንም ፓርቲዎች እወዳቸዋለሁ---ካርዴን ወስጃለሁ---ጊዜው ሲደርስ የምፈልገውን ፓርቲ እመርጣለሁ” ነው ያሉት ባልቴቷ፡፡ (የ2007 ምርጫ ምርጥ አባባል!!)       


Page 2 of 18