Saturday, 17 January 2015 11:36

ራሮት

“…አሁን ከቀኑ - ሰዓት ሆኗል፤ ዜና እናሰማለን!” የሚለኝ የለም
“በቅድሚያ አርዕስተ ዜናዎቹን” የሚል ድምፅ ግን ከጆሮዬ ይደርሳል፡፡ የለም ድምፅ አይደለም፤ መልዕክት በተሻለ ሁኔታ ይገልፀዋል፤ አዎ መልዕክት ነው፡፡
ይህ መልዕክት ከ’ኔ ዘንድ የሚደርሰውም “ሒሊፖፕ” ከረሜላ የሚመስለው ህፃን ቀለም ወደቤቴ ሲመጣ ነው፡፡
ይኸው መጣ!
“ጋሼ አስማረ?”
“አቤት”
“ባባዬ ነገ ዶሮ አያርድም!”
“ለምን?”
“አላርድም አለኝ”
“ለምን?”
“ዶሮ አይገዛም”
“በግ ሊገዙ ነው?”
“አይ”
“ቅርጫ ሊወስዱ ነው?”
“አይደለም”
“ታዲያ ለምንድነው?”
“አልገዛም አለኝ”
“ለምን?”
“እኔ…እኔ’ንጃ!”
በጭራሮ እጁ ዐይኑን አሸ፡፡ እጁን ሲመልስ በጣቶቹ መሀል ላይ ብይ አለ፡፡ ዐይኑን ነቅሎ በእጁ ያዘ እንዴ?! መሰለኛ!
የበዓል ዋዜማ ነው፡፡
ታዲያ ምን ነው?! አባ ባንተ ይርጉ ምን ሆኑ? እንዲያው ገንዘብ አጥሯቸው ይሆን?! ቤታቸው ልገኝ?
ግድ የለም ልረጋጋ፡፡ ረጋ ያለ መኪና ገደል አይገባም፡፡ ዝርዝር ዜናው ቤቴ ድረስ መምጣቱ አይቀርም፡፡
አዎ ልክ ነኝ፡፡ የምለው መሬት ጠብ አይልም፡፡ ምላሴ ዐይን አለው፡፡
ይኸው አባ ባንተይርጉ በሬን ተሻገሩ፡፡
“እንደምን አረፈድክ አስማረው?”
ሹራብ ኮፍያቸው ከአናታቸው አልወረደም፡፡
ዳለቻ ካኪ ሱሪያቸውም ከቦታው ነው፡፡
ሁሌ ዱላ የሚይዘው እጃቸው ባዶነት ግር እያለኝ፤
“ደህና አረፈዱ አባ?!” አልኳቸው፡፡
“ይመስገን ፈጣሪ!”
ከሸንበቆ የተሰራው ወንበሬ ላይ ከሲታ ገላቸውን አኖሩ፡፡
ለመሆኑ አባ ባንተ ይርጉ ማን ናቸው?!
አባ ባንተ ይርጉ የቀለም አባት መሆናቸውን መግለጥ አይጠበቅብኝም፡፡ ስለዚህ ሌላውን…
አባባ ባንተ ይርጉ የመንደራችን ጳጳስ ናቸው፡፡ መንደርተኛው የቀባቸው!
እንጂማ…እሳቸው ቤተ - መቅደስ የሚመላለስ እግር የላቸውም፡፡ ያላቸው ከአህያ ስር የሚሮጥ፣ የሚበር ክንፋም እግር ነው፡፡
እንጂማ …እሳቸው ‘ግዜአብሔርን ለማንቆለጳጰስ የሚሆን ዜማ የላቸውም፡፡ ያላቸው…ከአህዛብ ጆሮና ዐይን የራቀ ግን ከፈጣሪ ጋር የሚተቃቀፍ ዝምታ ነው፡፡
እንጂማ…እሳቸው ከመቅደስ ስጋጃ ላይ የሚንከባለል ፀአዳ ገላ የላቸውም፤ ያላቸው ከአዳፋ ገላቸው ስር ሆኖ ብርሃን የሚረጭ ሩህሩህ ልብ ነው፡፡
ዝምታ ያበዛሉ፡፡
ሰፈርተኛው ሁሉ’ሚያውቀውን አንድ ነገር ብቻዬን አውቃለሁ፤ አንደበተ ርቱዕነታቸውን!
ዝምታቸው ደንብሮ የሚሸሸው እኔን ሲያይ ነው፡፡
አንዳንዴ - “የንስሀ - አባታቸው እመስላቸዋለሁ እንዴ?” እያልኩ አስባለሁ፡፡
ህልማቸውን ሳይቀር የሚነግሩት ለ’ኔ ነው፡፡ ያንኑ ህልም የሚፈቱትም ለኔ ነው፡፡ ለመሆኑ እኔስ ማን ነኝ?!
እኔማ ወዛደር ነኝ፡፡
ሱፍ የማያውቁ፣ ኩንታል የሚናፍቁ ትከሻዎች ባለቤት!
ኩራት ‘ሚገላምጡ ስራ የሚያስሱ ዐይኖች አለቃ!
ይህን ያወቁት አባ ባንተይርጉ ከጨረቃ ቤታቸው አንዷን ፈንጠር ያለች ክፍል (ቤት) በወር 10 ብር አከራዩኝ፡፡ ተጐራበትን፣ ተዛመድን፡፡
“አለንጋዎት የት ደረሰች ዛሬ?”
“መንግስተ - ሰማያት!”
“ምን አሉኝ?”
“ምንም አላልኩህ ልጄ - ከሰማኸው ሌላስ”
ግንባሬን ቋጠርኩ፡፡
ሹራብ ኮፍያቸውን ከግንባራቸው ሽቅብ ገለቡት፡፡ ወደ አናቱ ላይ ሸጋታ ያበቀለ ጥቁር ጡብ አፈጠጠብኝ፡፡
“አለንጋዬ ፍቅር ተገለጠለት ልጅ አስማረ …መበደል አልሻም አለ፡፡”
“አልገባኝም አባ”
“አልገባህም? አዎ አይገባህም፡፡ አየህ ሰው ብዙ ጊዜ አይገባውም፡፡ ሰው ሳይሆኑ የሚሞቱ ሰዎች መብዛታቸው ለዚህ ነው፡፡ ሰው ሁሉ ሰው አይደለም ልጄ፡፡
የተከፈቱ ዐይኖች ሁሉ አያዩም፡፡ ከእየሱስ መምጣት በፊት ግብፅ የተከፈቱ ዐይን ነበራት ግን አታይም ነበር፡፡ ሙሴን በጨርቅ ጠቅልላ ጣለች፡፡ ክርስቶስ በቅዱስ እጁ ያን ዐይን ዳብሶ ገለጠው፡፡ ብርሃን ሆነ!”
ከነቢዩ መሐመድ በፊት አረቦች ክፍት ግን የማያይ ዐይን ነው የነበራቸው፡፡ ነቢዩ ኢብራሂምን ለእሳት ጥርስ አቀበሉት፡፡ ታላቁ ነቢይ በፍትህ አወቅ ድምጻቸው፣ ያ ዐይን ወደ ፍቅር እንዲመለከት አዘዙ፡፡ ሰላም ሆነ!
እንዲህ ነው ልጄ፤ ሰው ሁሉ ሰው አይደለም፡፡
ሙሉ መገለጥን የተጐናፀፍክ’ለት…ያኔ ሰው ትሆናለህ፡፡ የዐይንህ ቆብ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ፣ ወደ ኋላ፣ ወደ ፊትም ማየት ሳይከልልህ ሁሉን ስታይ!...ልብህ ዘሬ፣ ግንዴ፣ ሀገሬ፣ ወገኔ ሳይል ሁሉን ሲወድ ሲፈቅድ!
ግንድህ አዳም ነው፡፡ ዘርህ የሰው ዘር ነው፡፡ ሀገርህም ዓለም በመላ ነው፡፡ የምናውቀውም የማናውቀውም ዓለም በመላ፡፡ ፍጡራን በጠቅላላም ወገንህ ናቸው፡፡
ይህን ከተረዳህ ሰው ከመሆን ጥግ ላይ ደረስክ፡፡” ዝም ብዬ አዳመጥኩ፡፡ የገባኝንም ያልገባኝንም ዝም ብዬ አደመጥኩ፡፡ አባ…ረጅሙ ዕድሜያቸው ለሁለት ታጥፎ በድርብ ከኔ ነጠላ ዕድሜ ጋር እኩል ነው፡፡ ታዲያ የሚያውቁትን ግማሽ ቀርቶ ሩብም አላውቅም፡፡ ዕውቀት የሚባለው ነገር ሁሉ እኔ ካልጀመርኩት ግማሽ ይሆን የሚጀምረው?!
“እናም ልጅ አስማረ አለንጋዬን ጥዬአለሁ፡፡ ወገኔ የሆነን እንደኔው የሚተነፍስና የሚበላ ፍጡር ሸክም መጫን፣ ማሰቃየት ሀጢያት መሆኑ ተገለጠልኝ፡፡
አህያዬን እንዲሸጥልኝ ደባልቄ ደላላውን ልኬዋለሁ፡፡ ሸጦ መመለሱ አይቀርም”
“ሸጦ?”
“አዎ!”…በርግጥ ባልሸጥና እዚያ ሂዶ ሌላው ከሚያንገላታው እንዲሁ እረፍት ብሰጠው ብዬ ነበር፤ ሆኖም ይኼ በስተርጅና በኔ ሰበብ ወዲህ የመጣ ህፃንና ኑሮ ያጃጃትን እናቱን ረሀብ ሳስብ ወኔ አጣሁ፡፡”
መበስበስ የጀመረ ሙዝ የመሰለው የባለቤታቸው ፊት ዐይኔ ላይ ዋለለ፡፡
ሰውዬው ይግረሙኝ፣ ግራ ያጋቡኝ አልገባኝም፡፡
ፀጥታውን ለመገርሰስ ወዲያውም የቀለምን “አርዕስተ - ዜና” ዝርዝር ለማድመጥ በመሻት
“የበዓሉስ ዝግጅት እንዴት ነው አባ?” ስል ጠየቅሁ
“ምንም አይል!”
“ዶሮ ምናምኑን ሸመታችሁ?”
ዐይናቸውን ከቤቴ ወደ ውጪ አርቀው ወረወሩ፡፡
አንዳች ነገር ፈንክተው፣ ወይም ወግተው ወይም ስመው መለሱት፡፡
“አላስፈለገኝም፡፡”
“ምነው?”
ጉም የመሰለ ሪዛቸውን በጣቶቻቸው ቃኙ፡፡
“መቼ ነበር ልጄ?!…ግድ የለ ጊዜውን እንተወው…የትም ፈጭተን ዱቄቱን እናምጣው…ብቻ!
በህልሜ መሰለኝ፤ ዶሮ ላርድ ቢላዬን ሞርጄ ከአንገቱ ላይ አሰመርኩ፡፡
ቢላው አልቆርጥም ማለቱ! ስገዘግዘው …ስገዘግዘው…እምቢ አለ፡፡
ድጋሚ ሞርጄ ላርድ ሞከርኩ፡፡ አሁንም አሻፈረኝ አለ፡፡
እንዲሁ ፈጣሪ ሲመራኝ ድንገት ዶሮውን አየሁት፡፡ ይገርምሃል በትዝብት ዐይን እያየኝ ነበር፡፡ “ሰው ጨካኙ!” እያለኝ እንደሆነ አንዳች ኃይል ነገረኝ፡፡
“የለም ሰው ጨካኝ አይደለም” ብዬ ዶሮውን ለቀቅሁት፡፡
ህልም የእውነት ግልባጭ ነው ልጄ፤ ራዕይ ነው ያየሁት”
ከተቀመጡበት ተነሱ፡፡
“ከእንግዲህ ፈጽሞ አላደርገውም፣ ፈጽሞ ስልህ!
ነፍስ ያለው ፍጡር እንዴት ከመሰሉ ነፍስ ይነጥቃል?” ወጡ፡፡
ከሰዓታት በኋላ ዶሮ ገዝቼ ተመለስኩ፡፡ ሙያ ተኮር ችግር የለብኝም፡፡ ችግር ራሱ በጊዜ ከልቶታል፡፡ መናፍቅነት ስለሚሰማኝ ይሆን ለሌላ “ራሴ ማረድ ግን ብዙ አልደፍርም፡፡
እንደወትሮው ተጣራሁ፡፡
“አባ!...አባ ባንተርይርጉ!...አባ?!...ይምጡ ዶሮ ይረዱልኝ…!” ትዝ አለኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ አፌን በእጄ ተመተምኩ፡፡ ፊቴን አዙሬ የግራ ጐረቤቴ ደባልቄን በለሆሳስ መጣራት ጀመርኩ፡፡

Published in ልብ-ወለድ

በገጣሚ ብሩክታዊት ጐሳዬ የተጻፉ የግጥም ስብስቦችን ያካተተው “ፆመኛ ፍቅር” የተሰኘ የግጥም መድበል ከትላንት በስቲያ ምሽት በካፒታል ሆቴል ተመረቀ፡፡ የግጥሞቹ ጭብጦች በስደት ህይወት፣ በፍቅርና በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ በ80 ገፆች የተቀነበበውና 59 ያህል ግጥሞችን ያካተተው የግጥም መፅሃፉ፤ለአገር ውስጥ በ30 ብር፣ለውጭ በ10 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡
 “ኩራት በሀገር ልብስ” የፋሽን ትርኢት ተካሄደ
ሚራክል ዲዛይን እና ፋሽን ኢንስቲቲዩት ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ በአራት ወራትና በሰባት ወራት በዲዛይን ሙያ ያሰለጠናቸውን 154 ተማሪዎች ከትላንት በስቲያ ምሽት በሃርመኒ ሆቴል ያስመረቀ ሲሆን ተማሪዎቹም ስራዎቻቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ “ኩራት በሀገር ልብስ” በተሰኘ  የፋሽን ትርኢት ላይ 22 ሞዴሎች የተመራቂዎቹን የስራ ውጤቶች በመልበስ ፕሮግራሙን እንዳደመቁት የተቋሙ ዳይሬክተር ዲዛይነር ዳዊት መላኩ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ከ154ቱ ተመራቂዎች 32ቱ ነፃ የትምህርት እድል ያገኙና ከእነዚህ ውስጥ 8ቱ በሽመና ስራ ይተዳደሩ እንደነበር አቶ ዳዊት ገልፀው፣ ተቋሙ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ልብስ አምረውና ኮርተው እንዲታዩ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

    በአምስት አመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት በውስጥ አርበኛነታቸው የሚታወቁትን ወ/ሮ የሸዋረገድ ገድሌን የህይወት ታሪክ የሚዘክረው መፅሐፍ ዛሬ ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ ይመረቃል፡፡ “ሸዋረገድ ገድሌ፤ የአኩሪ ገድላት ባለቤት” በሚል ርዕስ የታተመው መጽሃፍ፤ ከ1878-1942 ስለኖሩትና በጣሊያን ወረራ ወቅት በዱር በገደሉ ላሉ አርበኞች  መረጃዎችን በማቀበል ታላቅ ገድል ስለፈፀሙት እናት አርበኛ ይተርካል፡፡ የመፅሐፉ ፀሐፊ ደራሲ ሺበሺ ለማ ሲሆኑ መጽሐፉን ያሳተሙት የአርበኛዋ የወንድም ልጅ ዶ/ር ክፍሌ ማርቆስ ገድሌ መሆናቸው ታውቋል፡፡ መፅሐፉ ለአገር ውስጥ በ70ብር፣ ለውጭ በ25 ዶላር ለገበያ የቀረበ ሲሆን በዛሬው የምረቃ ስነስርአት ላይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ሌተናል ጃገማ ኬሎ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

በታሪካዊቷ ደሴ ከተማ መሀል በሚገኘው ደሴ ህንጻ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ሲኒማ ቤት መከፈቱ ተገለፀ፡፡ “
ዙም ሲኒማ” ቤት 265 ምቹ መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን ኤች.ዲ ዘመናዊ ፕሮጀክተርና ዘመኑ የደረሰባቸው የድምፅ ቴክኖሎጂዎች ተገጥሞለታል፡፡
ሲኒማ ቤቱን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የጂታብ ኢንተርቴይመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጌታቸው፤ “ደሴ ካላት ረጅም ዕድሜና የከተማው ነዋሪ ለኪነጥበብ ካለው ጥልቅ ፍቅር አንፃር ደሴ እስካሁን እንዲህ ያለ ዘመናዊ ሲኒማ ቤት ሳታገኝ መቆየቷ የሚያስቆጭ” ነው ብለዋል፡፡
ዳራሹ ከሲኒማ በተጨማሪ እንደ ቴአትር፣ ስታንድአፕ ኮሜዲና  ሰርከስ ለመሳሰሉ ጥበባዊ ትርዒቶች ምቹ በመሆኑ በዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ቢመጡ አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል - አቶ ታዲዮስ፡፡ አስራ አንድ በአምስት (11x5) ሜትር ስፋት ያለው ዘመናዊ ስክሪን የተዘረጋለት አዲሱ ሲኒማ ቤት፤ ከጥር 16 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ስራ የሚጀምር ሲሆን የፊልም ፕሮዱዩሰሮች በሲኒማ ቤቱ ፊልማቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ ቀርቧል፡፡   

አርቲስት ደበበ እሸቱ ብቸኛው የህይወት ዘመን ተሸላሚ እጩ ሆኗል
በመጪው የካቲት የሚያካሂደውና በኢትዮ ፊልምስ ባለቤትነት የሚመራው የጉማ ፊልም ሽልማት ምርጥ አምስቶች ከትናንት በስቲያ በሃርመኒ ሆቴል ይፋ ሆኑ፡፡ በህይወት ዘመን ተሸላሚነት አርቲስት ደበበ እሸቱ ብቸኛ እጩ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በዕለቱ በ17 ዘርፎች በዳኞችና በተመልካች የተመረጡ አምስት አምስት እጩዎች የታወቁ ሲሆን ዘርፎቹም በምርጥ የተማሪ አጭር ፊልም፣ በምርጥ ድምፅ፣ በምርጥ ሙዚቃ፣ በምርጥ ስኮር፣ በምርጥ ሜክአፕ፣ በምርጥ የፊልም ጽሑፍ፣ በምርጥ ቅንብር፣ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ በምርጥ ተስፋ የተጣለባት ህፃን ተዋናይት፣ በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ህፃን ተዋናይ፣ በምርጥ ረዳት ሴት ተዋናዮች፣ በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ፣ በምርጥ ሴት ተዋናይት፣ በምርጥ ወንድ ተዋናይ፣ በምርጥ የተመልካች ምርጫ፣ በምርጥ ዳይሬክተርና በምርጥ ፊልም ጐራ በሚል ተከፋፍለዋል፡፡ መቶ ዳኞች በተሳተፉበት በዚህ ምርጫ ምርጥ አምስቶቹ የታወቁ ሲሆን በቀጣይ ከአንድ እስከ ሦስት የሚወጡት ተለይተው፣ የካቲት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ደማቅ የሽልማት ስነ ስርዓት እንደሚካሄድ የኢትዮ ፊልም መስራችና ስራ አስኪያጅ ዮናስ ብርሃነ መዋ ለጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡ ፕሮግራሙን ሙሉ በሙሉ ስፖንሰር ያደረገው በደሌ ቢራ ነው፡፡

በደራሲ ጀምስ አለን የተጻፈው “As the Man Thinknth” መጽሃፍ በመክብብ አበበ “ሰውና ሃሳቡ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የተተረጎመ ሲሆን  ዛሬ ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ በኢዮሃ ሲኒማ ቤት ይመረቃል፡፡ መፅሐፉ በሰው ልጆች ህይወትና አስተሳሰብ ላይ ለውጥ የሚያመጡ ሃሳቦችን የያዘ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ሰባት ያህል አበይት ርዕሰ ጉዳዮች ቀርበውበታል፡፡ በ48 ገጾች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ30 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩል በተመስገን መኮንን የተጻፈው “እርሱን ገዳይ” የግጥም ስብስብ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ በ78 ገጾች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ 80 ያህል ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን በማህበራዊ፣ በፍቅርና በፍልስፍና ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ የግጥም መፅሐፉ በ20 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በደራሲ ቃልኪዳን ሃይሉ የተጻፈው “ለምን አትቆጣም” የተሰኘ መፅሐፍ እንዲሁ ለንባብ የበቃ ሲሆን 30 ወጐችን የያዘው መፅሀፉ፤200 ገፆች ያሉት ሲሆን በ49 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ መጽሃፉ ለደራሲው ሁለተኛው ስራው ሲሆን ከዚህ ቀደም “የነጐድጓድ ልጆች” የሚል ልብወለድ  ለንባብ አብቅቷል፡፡
 በማኑ ዘ ጊዶሌ የተፃፈው “ስለ ሰዶም ዝም አልልም” የተሰኘ መፅሐፍም ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ መፅሐፉ በአገራችን እየተስፋፋ ስለመጣው የተመሳሳይ ፆታ ወሲብና በዚህ ዙሪያ የተለያዩ አገራት ያሉበትን አስጊ ሁኔታ ይተነትናል፡፡ መፅሐፉ በ143 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን በ50 ብር እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡ 

“ፈለግ” የስዕል አውደ ርዕይ በብሔራዊ ቴአትር ይከፈታል

በሰዓሊ ወርቅነህ ብዙ የተሰሩ ከመቶ በላይ ስዕሎች የሚቀርቡበት “The Big Picture Between You and Me” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ የፊታችን ማክሰኞ ከምሽቱ 12፡30 ጀምሮ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ይከፈታል፡፡ ስዕሎቹ የተለያየ ቅርፅና ይዘት ያላቸው ሲሆን የሰዓሊውን ብቃትና ፍልስፍና ያሳያሉም ተብሏል፡፡ አውደ ርዕዩ ከማክሰኞ ጀምሮ ለ11 ቀናት ለተመልካች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡
ሰዓሊው ከ12 ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ ፈለገ ስነስዕል ት/ቤት በአድቫንድስድ ዲፕሎማ የተመረቀ ሲሆን ከ “ሀበሻ አርት ስቱዲዮ” የስራ አጋሮቹ ጋር በመሆን  በፊንላንድ፣ በአሜሪካና በሌሎችም አገራት ስራዎቹን እንዳቀረበ  ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል ከስምንት ዓመት በፊት በአንጋፋዎቹ ሰዓሊያን እሸቱ ጥሩነህ እና አስናቀ ክፍሌ የተቋቋመው “ኢንላይትመንት አርት አካዳሚ” የነባርና አዲስ ተማሪዎች ስራዎች የሚቀርቡበት “ፈለግ” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ የፊታችን ረቡዕ በብሔራዊ ቴአትር አርት ጋለሪ ይከፈታል፡፡ የ20 ተማሪዎች ስራዎች በሚቀርቡበት አውደ ርዕይ፤ ለአምስት ቀናት ለተመልካች ክፍት እንደሚሆንና 45 ያህል ስራዎች ለእይታ እንደሚበቁም የት/ቤቱ ዳይሬክተር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡

       ዳሽን ቢራ ለሀገራችን የኪነ-ጥበብ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የታመነባቸውን ሥነ - ጽሑፍ (ግጥም) እና ኪነ-ጥበብ (ሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ) ለመደገፍ በየዓመቱ የሚካሄድ የ”ዳሽን አርት አዋርድ” ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡
ተወዳዳሪዎች ያሸልመኛል የሚሉትን ሥራቸውን ወሎ ሰፈር ሚና ሕንፃ፣ ሴንቸሪ ፕሮሞሽን ቢሮ እስከ ጥር 15 ድረስ ማቅረብ እንዳለባቸውና የሽልማት ሥነ - ሥርዓቱ ጥር 23  በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚከናወን የጠቀሱት የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ም/ሥራ አስፈጻሚ አቶ መክብብ ዓለሙ ዘመንፈስ፤ የውድድርና ሽልማቱ ዓላማ ኪነ-ጥበቡን ለማሳደግና ለመደገፍ ስለሆነ፣ ተወዳዳሪዎች ዳሽን ቢራን ሳይጠቅሱ ነፃ ሆነው በፈለጉት ርዕስና ሥራ መወዳደር እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡ ለአሸናፊ ግጥሞች ማሳተሚያም ድጋፍ እንደሚያደርጉ አክለው ገልፀዋል፡፡ ዳኞች ከደራስያንና ከሠዓሊያን ማኅበር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሙያው ከፍተኛ ልምድና እውቀት ያላቸው እንደተመረጡ ጠቁመው፣ 1ኛ የግጥም አሸናፊ 33ሺ ብር፣ 2ኛ 22ሺ ብር፣ 3ኛ 11ሺህ ብር እንደሚሸለሙ፤ በሥዕልና ቅርፃ ቅርፅም ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡት አሸናፊዎች ተመሳሳይ ሽልማት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ከ4ኛ እስከ 10ኛ የሚወጡት ደግሞ 1.500 ብር ይሸለማሉ ብለዋል፡፡ ዳሽን ቢራ የኪነ-ጥበብ ሽልማቱን ያዘጋጀው ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሆነ የጠቀሱት ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ካሁን ቀደምም በሕዝብ ተሳትፎ ት/ቤቶችና የጤና ተቋማት መሥራቱን፣ እስካሁን ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣቱን፣ ከዚህ ውጭ በስፖርት ዘርፍ ለባህርዳርና ለመቀሌ ስታዲየሞች የ26 ሚሊዮን ብር ድጋፍ፣ ለወልዲያ ስታዲየምም ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነና የኢትዮጵያን ስፖርት ለማሳደግ “ዳሽን ቢራ ስፖርት ክለብ” አቋቁመው በሁለቱም ፆታ እየተሳተፉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የእርሻና የኢንዱስትሪ ትስስርን ለማሳደግና የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ከአርሶ አደር ጋር በመተባበር በቢራ ገብስ ላይ ለምርምር፣ ለምርጥ ዘርና ለሥልጠና በጀት መድበው እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የገንዘብ አቅማቸው ደካማ (የድሃ ድሃ) ለሆኑ ሰዎች በጐንደር መኖሪያ ቤት መሥራት እንደጀመሩና በሌሎችም ስፍራ ተመሳሳይ ተግባር እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 17 January 2015 11:23

ሰባራ መስታወት

ወግ
“ከነታሪኩ ጋር ወደ ብረት ድልድዩ ሄድን” አለ በኩራት፡፡ የሁሉም ታላቅ ነው፡፡ ራሱን ጀብደኛ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ ቢያምኑትም ባያምኑትም ከእርሱ በላይ ያሉት ሲያደርጉት ያየውንና ሊያደርጉት ያቀዱትን ሰምቶ እንደራሱ ተግባር በቃላት አሳምሮ የመጠረቅ ተሰጥዖ አለው፡፡ ታናናሾቹ በእድሜ ከሚልቋቸው ታላላቆቻቸው ጋር ስለሚውል ይፈሩታል፡፡ አፍ አውጥተው አይናገሩ እንጂ ሁሉም ህፃናት እንደሱ ከትልልቆቹ ጋር መዋል አጥብቀው ይሻሉ፡፡ ይብዛም ይነስም የገነነ ምኞታቸውን በቅጥፈት ታሪክ እየለወሱ፣ ከእነርሱ ለሚያንሱት የመተረክ ጥልቅ ምኞት አላቸው፡፡
 ልጅነታቸው የበላይ ለመሆን ከመመኘት አላገዳቸውም፡፡ የሁሉም ታናሽ ትንሹ ልጅ ብቻ ታሪኩን እያዳመጠ በራሱ ሚጢጢ ዓለም ውስጥ ይላወሳል፡፡ አባቱ ሁሌም “ራስህን ሁን” ይለዋል ትንሹን፡፡
አባቱ ራሱ ባለፈ ህይወቱ ራሱን መሆን ያልቻለባቸው የክፉ ቀናት እጣ ላይ ወድቆ ያውቃል፡፡ ራስን ስለመሆን ማሰብ የጀመረው ተስፋውን ጥሎባቸው የተመሳሰላቸው ሰዎች ከውስጡ እንደ አየር በነው ከጠፉ በኋላ ነበር፡፡ ተስፋ ነፍስ የሚያኝክ ጥርስ ያለው ክፉ አውሬ ነው፡፡ ራሱን መምሰል መሆን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ሲያምን ልጁን፤
“ራስህን ብቻ ምሰል” ይለዋል እቅፉ ውስጥ ከቶ ፀጉሩን እያሻሸለት፡፡
“ራስህን ብቻ…”
ጠጠር ያሉ ቃላትን በመለማመድ ላይ ያሉት ትንንሽ ጆሮዎቹ ተቀስረው አባቱ የሚለውን ትንሹ ያዳምጣል፡፡ ራስ መሆንና ራስ መምሰል የሚሉ እንግዳ ቃላት ሲደጋገሙበት ትርጉሙን ሊያስስ በልጅ ደመነፍሱ ማሰብ ጀመረ፡፡ ምሉዕ ትንተና ባያገኝለትም “ራስህን ሁን” መባሉ ራሱን አለመሆኑን ነገረው፡፡ ራሱን መሆን እንዲረዳው ስለ ራሱ በቅጡ ማወቅ እንዳለበት አመነ፡፡ ራሱን ለማወቅ ደግሞ ሌሎችን መምሰል አማራጭ መስሎ ታየው፡፡ ውስጡ ይህን ነግሮታል፡፡ ራሱን የሚያይበት የመልክ መስታወቶቹ እኩዮቹ እንደሆኑ ስለገባው፣ በጥንቃቄ ራሱን እነርሱ ውስጥ መፈለግ ጀመረ፡፡ በወጉ ያልበሰለው አንጎሉ፣ ራሱን ያልተቋጨ ጅምር ሃሳብ እንደሆነ አስረዳው፡፡ ሙሉ እንዳልሆነ ሲገባው  ደመነፍሱ በድንጋጤ ተሸማቀቀ፡፡ ጎዶሎ ሆኖ መገኘት ተፈጥሮ ስፍራ የሰጠችን ነፍስ የሚያንዘፈዝፍ ቀዝቃዛ ፍርሃት ነው፡፡ እንጭጭ ፍርሃቱም ወደ ጠጣር ባይተዋርነት አደገ፡፡ የእድሜ አቻዎቹ መካከል ሆኖ ነፃነት የለውም፡፡ እንደነርሱ አይስቅም አይጫወትም፡፡
 የፍንደቃቸው ምስጢር ከሙሉነታቸው እንደመጣ ስለሚቆጥር፣ በሚሰበሰቡበት ስፍራ ሁሉ ደፍሮ መቀላቀል ይሳነዋል፡፡ ወኔውን አሰባስቦ ቢቀላቀላቸው እንኳን አያስታውሱትም፡፡ የሚከለልበትን ትከሻ ፈልጐ ከኋላቸው ሄዶ ይቀመጣል፡፡ ጀብደኛው የጀመረውን የጀብድ ታሪክ እየወሸከተ ያወራል፡፡
“እኔ…” አለ “…እጆቼን ዘርግቼ በድልድዩ ብረት ላይ ቀጥ ብዬ ቆሜ ተራመድኩ፡፡…” የተከፈተ አፋቸውን ከዝንብ እየተከላከሉ ያዳምጣሉ፡፡ ቃላቱ ጆሯቸውን አልፎ ልባቸው ጋ ሲደርስ ነጥሮ ይመለሳል፡፡ ትንሹ ግን በተከፈተ ጆሮው የሚሰማውን ወደ ውስጡ እያፈሰሰ ሌላ ግብዓት እያደረገው ነው፡፡ በፍርሃት ምክንያት የጎደለው እርሱነቱ እንዲሞላለት የሚሰማውን የድፍረት ታሪክ ወደ ማቆሪያው በፀጥታ ይቀዳል፡፡
“ቴዲ ሞክሮ አቃተው፡፡ በሆዱ እየተሳበ ሊሄድ ሲል ወድቆ ነበር፡፡ አሞራ ትመስላለህ ብሎኛል” አለ ፊቱ ላይ መንታ ገፅ እየታየ፡፡ እርካታና ውሸቱ እንዳይታወቅ የመስጋት መልክ በአንድ ላይ እንደ ቀለም ተደባልቆ ፈሷል፡፡ አድማጮቹ ግን ውሸቱን እንደሆነ ቢያውቁም ደፍረው አይናገሩትም፡፡ ለውሸት ጀብዱው የውሸት ፈገግታና አድናቆት እየለገሱት ይስቃሉ፡፡ እርሱ ታላቃቸው ነውና፡፡ እነርሱም እንደዚያ የማድረግ ገሃድ ያልወጣ ድብቅ ምኞትም ስላላቸው፡፡ ትንሹ ብቻ በባለታሪኩ ዓይን ውስጥ ያየውን እርሱነቱን በነፍሱ ጥርሶች እያኘከ ያደቃል፡፡ ከእነርሱ ጋር ሆኖም በጭምት ነፍሱ እንደተገለለ ነው፡፡ ፀሐይ እያሽቆለቆለች ወደ ሰንኮፏ ልትከተት ትንደረደራለች፡፡ ደመነፍሳቸው እየመሸ መሆኑን ሲነግራቸው እንኳን ማድመጥ አልፈለጉም፡፡ የቤተሰቦቻቸው ጥሪ ከተቀመጡበት እስኪቀሰቅሳቸው ይጠብቃሉ፡፡ “ትልቁ የዝግባ ዛፍ ላይ ወጥተን ደግሞ ከታሪኩ ጋር የጋጋኖ እንቁላል ይዘን ወረድን” አለ ጀብደኛው ልጅ፡፡ ትንንሾቹ ከራቀው ሰማይ ላይ የድፍረት እንቁላል ለማርባት እንደ ዝግባው የገዘፈ ምኞታቸውን በመሰላል ሲወጡ አፋቸው ለሃጭ ያረባል፡፡ ባለ ጀብድ ታሪኩ በዚህ እርካታ ይሰማዋል፡፡
ለዓይን ያዝ ማድረግ ሲጀምር ከየአቅጣጫው የወላጆች ጥሪ ተሰማ፡፡ በልምድ የአንዱ ወላጅ ጥሪ ለሁሉም እንደሆነ ቢያውቁም የራሳቸው ወላጆች እስኪጠሯቸው ይጠብቃሉ፡፡ ተፈላጊ ልጅ ብቻ ተነስቶ ይሄዳል፡፡ ያልተጠሩት ጊዜ ቸርችረው የቀራቸውን እንጥፍጣፊ የምሽት ጨዋታ ለመጫወት ጆሯቸውን አንቅተው መቆየት አለባቸው፡፡ ወላጆችም ከጐረቤቶቻቸው ጋር በጥሪው ይግባባሉ፡፡ አንደኛው ወላጅ ሲጣራ ሌሎቹ የእነርሱም ልጆች እስኪመጡ ጊዜ ይሰጧቸዋል፡፡ ሁሉም ሲበተኑ ያወሩትና የሰሙትን፤ የተወሰደባቸውንና የነጠቁትን ከጨለማው ጋር የነበሩበት ትተው ወደ ቤታቸው ይገባሉ፡፡ ቤት ውስጥ ደግሞ የሚጠብቃቸው ሌላ የልጅነት ህይወት ቅብብሎሽ አለ፡፡
ትንሹ ጆሮው የሰበሰበውን በሙሉ የዋህ ልቡ ላይ ቋጥሮ ይመለሳል፡፡ ሁሉም ጥለው የሄዱትን የሚያነሳው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሚጢጢ ልቡ አሻክራ የቀየጠችው እውቀት በድንገት ብልጭ አለለት፡፡ ራስን ሆኖ የመገኘት ብልሃት የተከሰተለት መሰለው፡፡ ራሱን ጀብደኛ ሆኖ አገኘ፡፡ የፍርሃት እውቀታችን ከሽፋኑ ሲገለጥ የሚወስደን ዓይናችን ወደሚያስተውለው ተጨባጭ ያልሆነ የምኞት ጥግ ነው፡፡ ራስን የመሆን የሙሉነት ፈተናውን ጀብደኞችን መስሎ እንደማያልፈው ተሰምቶታል፡፡ መልሱን ያገኘ በመሰለው ቁጥር ጥያቄውን ረሳ፡፡ የተጣመመው መልስ ቀጥ ያለውን የውስጥ ጥያቄውን አጣሞበት ከራሱ ጋር ተላለፈ፡፡ እነርሱን ሲመስል ራሱን መሆን አቆመ፡፡ ራስን አለመሆን ምንም ያለመሆን ብኩን የተፈጥሮ ምላሽ ይመስላል፡፡ እነርሱን መምሰል ራሱን ካለመሆን የጨለማ እስር ነፃ ያወጣዋል፡፡ ሆኖ ያለመገኘት ገመዱን እነርሱን በመምሰል ድርጊት ያለውል ቋጠረው፡፡ ዱባ መሆንን በመምሰል፣ ቅል አጠላልፎ እየገመደ፡፡ ነገ ለእኩዮቹ ተራኪ የሚሆነው እርሱ መሆን እንዳለበት እያሰበ፣ ከመንደራቸው ጀርባ ወዳለችው አነስተኛ ኩሬ አመራ፡፡ ሀሳቡ ደሙን አሙቆት እንፋሎቱ ገንፍሎ ወጣ፡፡ ልብሶቹን አወላልቆ ወደ ኩሬው ዘለለ፡፡ ዋኝቶ ባያውቅም ዛሬ እንደሚችል ምስጢረኛው ደመነፍሱ አረጋግጦለታል፡፡ አየሩ ላይ ሲንሳፈፍ፣ ነገ በድልድዩ ብረት ላይ እጆቹን እንደ አሞራ ክንፍ ዘርግቶ በድፍረት ስለመሄድ እያሰበ ነበር፡፡
 እንደአሁኑ በጨለማ ሳይሆን በደማቅ ብርሃን የሚንቁት እኩዮቹ በዓይናቸው እያዩት፡፡ በንቀት የተነፋ ልባቸው፣ ሲቀኑ በሚቀላ ዓይናቸው ውስጥ ሲፈነዳ የሚያገኘውን እርካታ እየተጠባበቀ፡፡
ኩሬዋ ለአዋቂ ጉልበት ታስባ ስያሜ ቢወጣላትም በህፃን ቁመት ባህር ሆና ስያሜዋንና ትንሹን ከጨለማው ጋር ተስማምታ ለመዋጥ ትችላለች፡፡ አባቱ “ራስህን ሁን” ሊለው መፅሐፍ የሚያነብበትን መነፅር ዝቅ አድርጎ ወደ ውጭ እየቃኘ፣ ልጁን በመጠበቅ ላይ ይሆናል፡፡ ያለፈ ዘመኑ ሌሎችን የመምሰል ባተሌነት በልጁ እንዲደገም ባለመሻት፣ የተጋረደ ማንነቱን ፍለጋ በሰባራ ዓይናቸው ውስጥ ስብርባሪ ገፁን በትዝታ እየለቀመ ይሆናል፡፡ ካለፈ ህይወቱና ከመፃሕፍት ባገኘው ድምር እውቀት መለኪያ ግን ልጁ ራሱን መምሰል አለበት፡፡ የአባትየው ትግል የልጁ መልክ ከሌሎች ፊት ጋር እንዳይመሳሰልበት ነው፡፡ ልጁ ሰዎች ራሳቸውን አዘቅዝቀው የሚመለከቱበት የተሰበረ መስታወት መሆኑ እስኪገባው ድረስ፡፡
(መሆሰል - መሆንና መምሰል ለማለት)   

Published in ጥበብ
Saturday, 17 January 2015 11:20

ከ“ኢጎ” ጋር 80 መቅደድ

“ይህንን መፅሀፍ ከደራሲው እውቅና ውጪ በከፊልም ሆነ በሙሉ ማባዛትም ሆነ ማሳተም በህግ ያስጠይቃል..” ገና የመፅሃፍን በራፍ ቆርቁረን ወደ ውስጥ እንደዘለቅን ፊት ለፊት የሚቀበለን የተለመደ የማስጠንቀቂያ ጽሁፍ ነው፡፡
ጁዲ ክሪሽናሙርቲ የሚባል ህንዳዊ ፈላስፋ ግን ማስጠንቀቂያውን ባልተለመደ ሁኔታ ወደ ስጦታ ቀይሮታል:: Freedom from the Unknown በሚለው መጽሃፉ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ እንዲህ ይነበባል:- “መፅሃፉን ማባዛት ፣ ማሳትም እና የባለቤትነት መብትንም መውሰድ ይቻላል። መፅሀፉ የተጻፈው በነፍስ ነው፤ የነፍስ ኮፒራይት ደግሞ የሁሉም ነው” ይላል።
ይህን ፈላስፋ ከመጽሀፉ ጀርባ ፎቶውን ለምን እንዳላኖረ ብንጠይቀው የሚሰጠንን ምክንያት ለመገመት አይቸግረንም። “ይህ ስራ የነፍስ ስለሆነ ፎቶ የለውም፣ ለነፍስ የሚሆን ካሜራ ካላችሁ አንስታችሁ ለጥፉበት።”……..አንደበቱ ከእዚህ ውጪ ሊያፈልቅ አይችልም። ኢጎን……….የቀበረ ብጽሁ ሰብእና ከዚህም በላይ…ብጽህናን….ለመታደል እጅ አያጥረውም።
ኢጎ በጊዜ ሂደት እንደ እንግዴ ልጅ እላያችን ላይ  የሚበቅል አዚም ነው። ተቆርጦ ቢጣል እፎይታ፤ ቢዛመዱት ደግሞ ሰላም የሚያርቅ ጠንቅ፣ ለበረሀ ካባ፣ለቁር እራፍ፣ጥሎ የማያስጥል አሳሳች፣ አጓጉል ስሜት ነው። ከአይን ርቆ ሲያዩት መዓዛው የሚያውድ ውብ ተፈጥሮ ይመስላል። ሲቀርቡት ህይወት አልባ በድን አርቴፊሻል አበባ ሆኖ ይገኛል። የደም ዝውውር፣ ሙቀትንና እስትንፋስን የተነፈገ በድን፣ በአምሳላችን የተቀረጸ ጭምብል ነው። በጭምብሉ እያጮለቁ መጭበርበር ይቻላል። ጭምብሉን ወግድ ብሎ አይንን እርቃንን ከፍቶ አካባቢውን መቃኘትም እንዲሁ። ምርጫው በእጃችን ነው። ወደ እሳት ወይም ወደ ውሀ።
ሶቅራጠስ የሞት ፍርድ ከተበየነበት በኋላ የመጨረሻ መልእክቱ ይህ ነበር:-
“ክፋት እና ሞት ለየቅል ናቸው። ክፋት ብርታትን አለቅጥ ታድሏል። ጉልበቱ እንደ ሰንጋ ፈርስ ነው። ከእርሱ ጋር የምሽቀዳደምበት አቅም የለኝም። እንደምትመለከቱኝ እድሜዬ ሸሽቷል፣ ጡንቻዬም ሟሽሿል። ጉልበቱና አቅሙ ያላቸው ይሽቀዳደሙት። አቅሜ የሚፈቅደውን ደካማውን ሞት መርጫለሁ።” ኢጎ የክፋት የጡት አባት ነው። ክፋትን ከደረቱ ጡት እንዲጋት፣ ከጉያው ሙቀት እንዲምግ ያለስስት ይጋብዘዋል። ከቡቃያነቱ አንስቶ ጥላ ከለላ ይሆንለታል። እንደሶቅራጠስ ያለ ብጽህና በኢጎ ፊት ስላቅ ነው። ከሚድህ ጨቅላ አእምሮ የሚመነጭ’ለበኩር ልጅነት የማሳጭ የማያዛልቅ ጸሎት።
አብርሀም ሊንከን  ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድሮ ካሸነፈ በኋላ የመጀመሪያ ንግግር ለማድረግ ገና ወደ መድረክ ሲወጣ፤ አንድ ግርማ ሞገስ የራቀው ከበርቴ በጩኸት ጉባኤውን ያደፈርስ ጀመረ:-
 ”ስማ …….በለስ ቀንቶህ እንደራሴ ሆንክ ማለት የምስኪን ልጅነትህ ይፋቃል ማለት አይደለም። አባትህ ጫማ ጠጋኝ ነበር። እንደውም በእዚህ ጉባኤ ከታደምነው የምክር ቤት አባላት አብዛኞቻችን የተጫማነው ጫማ በአንተ አባት የተበጃጀ ነው። እናም የመጣህበትን ጉሮኖ አትዘንጋ ”አለ እያፌዘ፡፡ አብርሀም ሊንከንም ይህንን ጎርባጭ  ፌዝ በሚገርም ሁኔታ ወደ ቁምነገር እንዲህ ለወጠው:- “ወዳጄ፤ የአባቴን ስራ ስላስታወስከኝ በእጅጉ አመስግንሃለሁ። እርግጥ ነው አባቴ ጫማ ሰፊ ነበር። እጅግ በጣም ፈጠራን የታደለ፣ቢፈጥር ቢፈጥር የማያልቅበት፣እኔ እንኳን እዚህ ደረጃ ላይ ደርሼ የእርሱን አንድ እጅ ችሎታ ልተካከል አልችልም። በእውነት….ዛሬ የምክር ቤቱ አባላት በሙሉ የተጫሙት ጫማ በአባቴ ታታሪ እጆች የተበጃጁ እንደሆኑ በመበሰሬ ልዩ ስሜት ነው የተሰማኝ፤ ደስታዬን እጥፍ ድርብ ላደረገልኝ  ለእዚህ ቀናኢ ወደጄ ደግሜ እጅ እነሳለሁ፡፡” አለ
የአብርሀም ሊንከን መልስ ለከበርቴው ዱብ እዳ ነበር። ሽንቆጣው ስሜቱን ያሳምመዋል ብሎ ሲጠብቅ ጭራሽ የምስጋና ጋጋታ አዥጎደጎደለት፡፡ በእዚህ ጊዜ ከበርቴው ግር ተሰኘ፤የአብርሃምን ጤንነት ክፉኛ ጠረጠረ፤ በእርግጥም ለኢጎ ጤንነት ማለት መታመም ፣መብከንከን፣ መቆጨት፣ በትናንትና ተረት ተረት መሸማቀቅ ነው። ኢጎ የጥድፊያ ብይኑን ለመስጠት አባይ ሆኖ አያውቅም፡፡ በሰካው አዳፋ መነጽር እየታገዘ ሁለመናህን ይሰልልህ እና በመነጽሩ መስታወት ላይ ያረፉትን ጉድፎች የአንተ መገለጫ ያደርጋቸዋል። በዳበሳ በደምሳሳው ይፈርጅሃል። ጅምላ ፍርጃ ከኢጎ የሚጠበቅ ግብር ነው። ከበርቴው ከአብርሀም የድህነት ታሪክ ተነስቶ አንድ ጥግ ይዞ ነበር። ስለ አብርሀም ማንነት አስቀድሞ ስለፈረጀ ፍሬ ይኖረዋል ብሎ አልጠበቀም።
ከበርቴው በራሱ ጥሩ ነው። የተሳረረው መናኛ አባዜ ግን ክፉነቱን አጋነነበት። ወዶ አይደለም። ክፉ አባዜውን ከውስጡ ለይተን ብናወጣው የሚቀረው ቅድስናው ብቻ ይሆናል። አዞ ግራ ተፈጥሮን አብዝቶ የታደለ አውሬ ነው። እየበላ ያነባል። ገና ለማላመጥ አፉን ወዲህ ወዲያ ሲያላውስ ዘለላ እምባዎቹ በግራ እና በቀኝ ጉንጮቹ ላይ ዱብ ዱብ ይላሉ። የአዞ እምባ አንዳንዴ የሰው ግብርንም መግለጫ ይሆናል። እየበሉ ለሚያነቡ፣ ከአንገት በላይ ርህራዬአቸውን ለሚያውሱ ተዋናዮች የሚመጥን አባባል ነው። ሌላም ግራ ተፈጥሮ አለው። አባት አዞ የተወለዱ ግልግል ልጆቹን ለመስልቀጥ ማንም አይቀደመወም። እናት አዞ የአብራኩን ክፋዮቹን በስል ጥርሶቹ ለመቀርጠፍ ከሚጣደፈው ስግብግብ ባሏ ለመከላከል እንደምሽግ የምትጠቀመው አፏን ነው። ግልገሎቿን ከአፏ ውስጥ አኑራ በቻለችው አቅም ከጥቃት ለመከላከል ትሞክራለች። እንዲህ እንዲህ እያለች እድለኛ ከሆነች ከደርዘን ግልገሎቿ መካከል ሶስት ወይም አራቱ ይተርፉላታል። ካልቀናትም ሁሉንም ታጣቸዋለች።  
እንግዲህ አባት አዞ ለአብራኩ ክፋዮች የሚራራ አንጀት ያጣው ፈቅዶ አይደለም። ተፈጥሮ ባኖረችለት አልባሌ ሰብእና እንጂ። ይህን ሰብእና  ከውስጡ በሆነ ተአምር ማስወገድ ቢቻል የእናት አዞ ባህሪን ተላብሶ እናገኘዋለን። ደንዳና አንጀቱ ወደ እርብትብትነት ይቀየራል። የግልገሎችን ወገብ ለመበጠስ የሚሰናዳው አፉ ይለጎማል። የከበርቴው ግብር በአባት አዞ ይመሰላል። ኢጎ ነጭ ላብ እስኪያልበው ላይ ታች የሚባትለው ሁሉም ሰው አባት  አዞ ሲሆን ለመመልከት ነው። ስግብግብነትን ፣ጭካኔን እና ክፋትን  የተወዳጀ አውሬ ለማድረግ። ከበርቴው የአብርሃም ሊንከንን “ክብር“ ለመቀርጠፍ ጎሬ አፉን እየከፈተ ነበር። የኢጎ ክብር የነጠፈበትን ሰው፤ ኢጎ ክብርና ቁብ የማይሰጠውን ሰው ግን እንዴት መጉዳት ይቻላል። የከበርቴው ከርሳም አፉ እንደተከፈተ ቀረ። ከጥርሱ የተሰነቀረው ግዳይ ምራቅ የሚያስውጥ አልነበረም። ሸክሙ የቀለለትን ቀላል ፍጡሩን አላምጦ ከአንጀቱ እንዴት ጠብ ይበልለት። በአፉ ላይ ሊቀመጥ የማይችል ነጥብ ፍጡር፣ እጅግ በጣም ቀላል ፍጡር፣ሚዛን የማያነሳ ውሀ የማይቋጥር ደቃቃ ፍጡርን ለማላመጥ ጥርሶቹ የበይ ተመልካች ሆኑበት።
ሰሞኑን በአንድ መጽሄት የፊት ገጽ ላይ በወጣው ውብ ፎቶዋ የተነሳ ስልኳ እረፍት ናፍቆታል። የአድናቂው ብዛት ትንግርት ነው። ይህ ፎቶ ..ያ.. የሞደሌነቷን፣ የፍሰሃውን ዘመን በምናብ እያንሸራሸረ የሚያስኮመኩማት ታንኳዋ ነው። በፎቶው ላይ ለአማላይ ገላዋ ስስ ሚኒ፣ እንደ መቃ ለተሰደረው አንገቷ አይነ ግቡ “ስካርፍ” ፣ለባቷ ግነት ረጅም ቡት ጫማ ተጫምታ እንደ ጨረር በሚዋጉ ዶቃ አይኖቿ ቡዝዝ ብላ ታስተውላለች። አሁን ግን ያ ሁሉ ውበት ተረት ሆኗል፡፡ በቆዳዋ ላይ እርጅናን የሚያሳብቁ የተጋደሙ የደምስሮች እዚህም እዚያም ይታያሉ። አሁን ምንም የለም። ቁንጅና ዳሌ በእድሜ ገመድ ተተብትበው መቀመቅ ወርደዋል። ሽብሽብ ቆዳን ተከናንባለች። በእርጅና ሱባኤ እየተፈተነች ነው። አድናቆትን መጾም ከጀመረች ብዙ አመታት ተቆጥረዋል። ሰሞኑን ግን ከሱባኤው የሚያስተጓጉል ሁነኛ ነገር ነው የገጠማት። ቁዘማን የሚያስገድፍ፣ ከተነፋፈቀችው ወጣትነቷ ጋር ዳግም የሚያስተቃቅፍ ሁነኛ ገጠመኝ። ውብ ፎቶዋ እርሷን ተክቶ አለሁ አለሁ እያለላት ነው። አድናቂዎቿን ከየሸጡ እየሳበ የረሳችውን ትኩረት በላይ በላይ እየመገባት ነው። በእዚህም ልቧ ጮቤ መርገጥ ጀምሯል። ምን ያደርጋል…………….ብዙም ሳትቆይ የቆፈን ድባብ ይሰፍርባታል። ከእያንዳንዱ አድናቂ ጋር በስልክ የቃላት ልውውጥ ካደረገች በኋላ ስቅስቅ ብላ ታነባለች። በምስል ላይ የቀረው ውብነቷ እያባባት ሙሾ ታወርድለታለች። ሙሾ ላጣችው ገላ፣ እኔነቴ ማንነቴ ብላ ለተጣበቀችበት ሰብእና፣ በጊዜ ንፋስ እየተንሳፈፈ ከአይን ለሚሰወር እፉዬ ገላ፣ ታነባለች፤ ደረቷን ትደቃለች።ኢጎን እቺን ሴት ራሱ ባነጠፈው ሃዲድ ላይ እንዳሻው ያነጉዳታል። ወደ ትናንትና ይመልሳትና ምስሏን አሳልሞ ከአሁኑ  ከሞሸሸው ገላዋ ጋር ፊት ለፊት ያጋፍጣታል። በንጽጽሩ ትብከነከናለች። ከኢጎ ጋር በመሰረተችው ሶስት ጉልቻ ጸጸት የሚባል የበኸር ልጅ አፍርታለች። ከራሷ ጋር መቆራቆስ የአዘቦት ግብሯ ነው። ትናንትን እየኖረች በአጣችው ትብከነከናለች። የያዘችው ጉም ነው። ፊት ለፊቱ ጨፍግጎባት በደመነፍስ እድሜዋን እየገመደች የምታከትም ምስኪን ምርኮ ሴት።  ከ ኢጎ ጋር ሰማኒያ ካልቀደድን፣ትዳር ለምኔ ብለን ካላመጽን፣ የምናዘግምበት ጎዳና በአሜኬላ የተሞላ ጠዝጣዥ የጣት ላይ ቁስል ሆኖ እድሜያችንን በሙሉ ገመምተኛ ሆነን እንድኖር ይፈርድብናል።

Published in ጥበብ