ኢትዮጵያና ናይጄርያ ወደ ዓለም ዋንጫ ጥሎ ለማለፍ የገቡት ትንቅንቅ ከወር በኋላ በመልስ ጨዋታ ይለይለታል። ዋልያዎቹ በናይጄርያዋ ከተማ ካላባር በሚገኘው ዩጄ ኡሱዋኔ ስታድዬም ህዳር ሰባት ለሚያደርጉት ፍልሚያ ዝግጅቱን ትናንት ጀምረዋል፡፡ በመልሱ ጨዋታ ናይጀሪያ ለ5ኛ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ለመብቃት ስታነጣጥር ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን በመወከል የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ማግኘቱን ታልማለች፡፡
ናይጄርያ በአዲስ አበባ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ኢትዮጵያን 2ለ1 ካሸነፈች በኋላ የማለፍ እድሏን እንዳመቻቸች ሲገለፅ፤ በሌላ በኩል በኳስ ቁጥጥር እና በጨዋታ ናይጄርያ ላይ ብልጫ ማሳየቱ የተነገረላት ኢትዮጵያ የማለፍ ተስፋዋን ከሜዳው ውጭ የምተወስንበት አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች። ናይጄርያ ኢትዮጵያን 2ለ1 ካደረገች በኋላ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ 27ኛ ግጥሚያዋን በማሸነፍ በአፍሪካ ደረጃ በብዙ ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ክብረወሰን ሆኖላታል፡፡ ናይጄርያ በካላባር በምታደርገው ጨዋታ ተሸንፋ አለማወቋ በመልሱ ትንቅንቅ የኢትዮጵያን ፈተና ያከብደዋል፡፡ የእግር ኳስ ዘጋቢው ድረገፅ ጎል ዶት ኮም በመልሱ ጨዋታ ማን ያሸንፋል በሚል ጥያቄ አንባቢዎቹን አሳትፎ በሰራው የውጤት ትንበያ አሸናፊነቱ 76.2 በመቶ ለናይጄርያ 23.8 በመቶ ለኢትዮጵያ ግምት ተሰጥቷል፡፡ 3ለ0 ፤ 1ለ0 እና 3ለ1 ናይጄርያ እንደምታሸንፍ የጎል አንባቢዎች ተንብየዋል፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በመልሱ ጨዋታ የማሸነፍ እድል መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ እንዳሳየነው የኳስ ብልጫ ናይጄርያን በሜዳው ስንገጥም ከፍተኛ ትግል አድርገን 2-0 አልያም 2-1 ማሸነፍ እንችላለንም ብለዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በቀሪው 1ወር በሚኖራቸው ዝግጅት የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያስፈልጋቸው ያስታወቁ ሲሆን ለቡድኑ የማለፍ እድል ቀላል ግምት መሰጠት እንደሌለበት በማሳሰብ ከትልቅ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻው እንዲዘጋጅላቸው ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በበኩሉ በተገኘው ድል የተሰማውን ደስታ በገለፀበት ወቅት ‹‹ያሸነፍነው እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ ነው፡፡ በተለይ በጨዋታው ያደረግኳቸው ሁለት ቅያሪዎች ግጥሚያውን ወደራሳችን አጨዋወት በመቀየር ድላችንን ለማረጋገጥ ምክንያት ሆኖልናል፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ ስቴፈን ኬሺ ለመልሱ ጨዋታ አዲስ እቅድ በመንደፍ እንሰራለን ብሎ በተናገረበት ወቅት ናይጄርያውያን ከኢትዮጵያን ድጋፍ አሰጣጥ ተምረው በካላባር በሚደረገው ጨዋታ ስታድዬሙን በነጭ እና አረንጓዴ ቀለሞች በማሸብረቅ እንዲደግፉ ጥሩ አቅርቧል፡፡
ናይጄርያ ከኢትዮጵያ ጋር ከምታደርገው ጨዋታ በፊት ከዮርዳኖስ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ታደርጋለች፡፡ ከመልሱ ጨዋታ ሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በለንደን ከተማ በሚገኘው የፉልሃም ክለብ ስታድዬም ክራቫን ኮቴጅ ከአራት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮኗ ጣሊያን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ እቅድ ይዛለች፡፡ ይህን የወዳጅነት ጨዋታ የናይጄርያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ያዘጋጀው በዓለም ዋንጫ ከሚያደርገው ዝግጅት ጋር በተያያዘ 2013 ከመገባደዱ በፊት ከዓለም አስር ምርጥ ቡድኖች ከአንዱ ጋር ንስሮቹ መጫወት እንዳለባቸው አቅዶ ሲሰራ በመቆየቱ ነው፡፡
የጨዋታ ብልጫ፤ የዳኝነት በደልና መረብ ያልነኩት ኳሶች
በዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታድዬም ኢትዮጵያ ከናይጄርያ የተገናኙበት የመጀመርያ ጨዋታ በአፍሪካ ዞን ከተደረጉ ሌሎች 4 ጨዋታዎች አነጋጋሪው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው ግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አስደናቂ አጨዋወት በማሳየት ናይጄርያን በከፍተኛ ደረጃ አጨናንቆ ነበር፡፡ ዋልያዎቹ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ከሶስት በላይ ጎል የማግባት እንቅስቃሴዎች በናይጄርያ የግብ ክልል አድርገዋል በአጨራረስ ድክመት ከመረብ ለማዋሃድ አልሆነላቸውም፡፡ በ23ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰይድ ከመሃል የተሻገረለትን ኳስ የናይጄሪያ ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ወደ ግብ መታ፡፡ ኳሷ የናይጄርያውን ግብ ጠባቂ ኢኒዬማ አምልጣ የግቡን መስመር ብታልፍም የናይጄሪያ ተከላካይ ከጐል ውስጥ አወጣት፡፡ በዚያች ቅፅበት ሳላዲን ሰይድ ደስታውን እየገለፀ ነበር፡፡ ካሜሮናውያኑ የመስመር እና የመሃል ዳኞች ግን ተነጋግረው ጎሏን ሳያፀድቋት ቀሩ።

ይህች የግብ አጋጣሚ መበላሸቷ የዋልያዎቹን በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት እና በስታድዬም የነበረውን ደጋፊ ስሜት አዘበራረቀ፡፡ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተደረገው አስደንጋጭ ሙከራ በሳላዲን ሰይድ ነበር፡፡ በግራ መስመር ወደ ግብ የመታትን ኳስ ኢኒዬማ በአስደናቂ ብቃት አድኗታል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ዋልያዎቹ በማጥቃት ጨዋታቸው በናይጄሪያ ቡድን ላይ ተደጋጋሚ ጫናዎችን በመፍጠር ቀጠሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይም በ57ኛው ደቂቃ ላይ በሃይሉ አሰፋ በግራ መስመር ናይጄርያ ክልል ውስጥ ገብቶ ኳሷን ወደ ግብ ክልል አሻገራት። የናይጄሪያው ግብ ጠባቂ ቪንሰንት ኢኒዬማ ኳሷን ሲይዛት የግብ መስመሩን በሙሉ ሰውነቱ አልፎ ገብቶ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የመስመር ዳኛው ጎሏ እንደገባች በማሳወቃቸው ወዲያወኑ የመሃል ዳኛው ግቧን በማፅደቅ ኢትዮጵያ 1ለ0 መምራት ጀመረች፡፡ ጎሏ በስታድዬም የነበረውን ደጋፊ ከማነቃቃቷም በላይ በናይጄርያ ቡድን አቋም ላይ መሸበርን የፈጠረች ነበረች፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ማንም ባልጠበቀው ውሳኔያቸው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የዋልያዎቹን አጨዋወት የሚያውክ የተጨዋች ቅያሪ አደረጉ። በመሃል ሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየውን አዳነ ግርማን በአጥቂው ኡመድ ኡክሪ ቀየሩት፡፡

ተጨማሪ ጐል ዋልያዎቹ እንዲያገቡ ከመፈለግ አንፃር ነበረ፡፡ ይህ የተጨዋች ለውጥ በብሄራዊ ቡድኑ አጨዋወት ላይ የፈጠረው ተፅእኖ ቀላል አልነበረም፡፡ ከአዳነ መውጣት በኋላ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ የመሃል ሜዳውን ለመቆጣጠር ሁለት ተጫዋቾች በአስር ደቂቃዎች ልዩነት ቀይሮ አስገባ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይም በ67ኛው ደቂቃ ላይ ኢማኑዌል ኤሚኒኬ ከመሀል ጀምር ኳስ በመግፋት ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ወደግብ አክርሮ መታ፡፡ ድንገተኛዋን ኳስ ያልጠበቀው ጀማል ጣሰው ሊያድናት የቻለውን ያህል ቢወረወርም ናይጄሪያውያን አቻ ያደረገች ጎል ሆነች፡፡ ጨዋታው 1 እኩል በሆነ አቻ ውጤት ቀጠለ፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት በአዳነ ቅያሪ የሳሳውን አማካይ መስመር ለማስተካከል በሚመስል ውሳኔ ሽመልስ በቀለን በማስወጣት አዲስ ህንፃ እንዲቀየር አደረጉ፡፡ ይሁንና ይህ ቅያሬ ናይጄርያውያን ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት የጀመሩትን የተጠናከረ እንቅስቃሴ የመገደብ አቅም አልነበረውም፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ኢማኑዌል ኢሚኒኬ ተከላካዩን አይናለም ሃይሉን በማለፍ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ገባ፡፡ አይናለም ያመለጠው ኢሚኒኬን ማልያ ጎትቶ በማስቀረቱ ዳኛው የፍጹም ቅጣት ምት ለናይጄሪያ ሰጡ፡፡ ወዲያውኑ ኢማኑዌል ኢሚኒኬ ለራሱና ለቡድኑ ሁለተኛውን ጐል በቀላሉ ለማስቆጠር ችሏል።
ከኢትዮጵያና ናይጄሪያ ጨዋታ ማግስት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሐናት የዋልያዎቹ አጨዋወት ቢደነቅም በግብ ክልል ወሳኝ የጐል አጋጣሚዎችን በመፍጠር ቡድኑ የተዳከመ መሆኑ ለሽንፈት ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዋልያዎቹ ማራኪ የኳስ ቅብብልና ቁጥጥር በማሳየት የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆኑትን ንስሮቹን ማስጨነቃቸው እና ከተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ምርጥ ተጫዋቾች የተሰባሰቡበትን የናይጄርያቡድን በመግጠም ልዩ ብቃት ማሳየታቸው ስፖርት አፍቃሪ የገጠመውን ሽንፈት በፀጋ እንዲቀበል ያስቻለ ነበር፡፡ የሱፕር ስፖርት ዘጋቢ ስለጨዋታው ባሰፈረው ትንተና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአጨዋወታቸው በኳስ ቁጥጥር ተሽለው ቢታዩም ለጎል የሚበቁ የመጨረሻ ኳሶችን በማቀበል ውጤታማ እንዳልነበሩና ይህን ውጤት አልባ እና ተረከዝ የበዛበት የኳስ ቅብብል ለሰርከስ ካልሆነ ውጤት ለሚያስፈልገው ወሳኝ ግጥሚያ ማድረጋቸውን አሰልጣኙ ማረም ነበረባቸው ብሏል፡፡ በአዲስ አበባው ጨዋታ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች ቡድናቸው በሜዳው ሁለት ለአንድ መመራት ጀምሮ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ 23 ደቂቃዎች እየቀሩ ሊያበረታታ ከሚችል ድጋፍ መቆጠባቸው እንዳሳፈረው በትንተናው የገለፀው ዘጋቢው በስታድዬሙ ከ35ሺ የዋልያዎቹ ደጋፊዎች ይልቅ በመቶዎች የሚቆጠሩት ናይጄርያውያን ጩሀት ጎልቶ መሰማቱን እንደታዘበ አብራርቷል፡፡
የናይጄርያ የስፖርት ሚኒስትር ንስሮቹ የሚገባቸውን ድል እንዳስመዘገቡ የተናገሩት እንደአፍሪካ ሻምፒዮን ተጫውተው የመጀመርያውን ምእራፍ እንደዘጉ በማስገንዘብ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተገኝተው የነበሩት ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን ቡድናቸውን ከጨዋታ በፊት በመጎብኘት ማበረታቻ ማድረጋቸውንም አመስግነዋል። በናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ የነበሩት ፋቲ አማዎ ንስሮቹ ለመልሱ ጨዋታ እንዳይዘናጉ አስጠንቅቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ያልተጠበቀ ድል የማስመዝገብ አቅም እንደሚኖራቸው በማሳሰብም ለዓለም ዋንጫ የመድረስ እድላችው ገና 75 በመቶ የተረጋገጠ በመሆኑ ለሚቀረው የ90 ደቂቃ ጨዋታ አቻ ለመውጣት ወይም ለማሸነፍ ታስቦ መሰራት አለበት የሚል ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ ሌላው የቀድሞ የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኦገስቲን ኢግዌቨን እንደተናገረው ደግሞ ናይጄርያውያን የአዲስ አበባውን ጨዋታ ድል ሊያደርጉ የቻሉት ባላቸው ልምድ ከኢትዮጵያ የተሻሉ ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በኳስ ቁጥጥር የላቁ እንደነበሩ የመሰከረው ኢግዌቨን በመልሱ ጨዋታ ንስሮቹ ሃላፊነታቸውን አሳክተው መጨረሳቸውን እጠብቃለሁ ብሏል፡፡
ከዋልያዎቹ አስደናቂ አጨዋወት ባሻገር በከፍተኛ ደረጃ ያነጋገረው በካሜሮናዊው ዳኛ የተሻረው የሳላሃዲን ሰኢድ ግብ ነበር፡፡ በጨዋታው ማግስት ይህ ጎል ፀድቋል ተብሎ ግራ መጋባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሰኞ አመሻሹ ላይ ኢትዮጵያ አቻ ሆናለች በሚል የተናፈሰው መረጃ ሃሰት ነበር። መስመሩን እንዳለፈች በብዙ ዘገባዎች የተወራላት ጎል ትክክለኛ ብትሆን እንኳን ጎሏን ያላፀደቀው ዳኛው መቀጣቱ እንጂ ጎሉ የሚፀድቅበት ሁኔታ አልነበረም ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ይህን በተመለከተ የክስ ማመልከቻውን ለአለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ አቅርቦም ነበር። ፈፋ ለፌደሬሽኑ በላከው ምላሽ በመተዳደሪያ ህጉ አንቀፅ በመጥቀስ ክሱን ተቀባይነት እንደሌለው አሳውቋል፡፡ ቪንሰንት ኢኒዬማ ለኢትዮጵያ የተመዘገበችው የመጀመርያ ጐል ብዙዎች እንደሚያስቡት የግብ መስመሩን አላለፈችም ብሎ በልበሙሉነት የተናገረው በጨዋታው ማግስት ነው። “እንደ እኔ አቋም ግብ አልነበረችም፡፡ ለምን እንደተሰጠ አላውቅም፡፡ ኳሷን የያዝኳት መስመሩን አልፋ አይደለም። የመስመር ዳኛው እንዴት ጐሉን እንዳፀደቀ መረዳት አልቻልኩም” ሲልም አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ ተሽሮበታል ስለተባለችው መረብ ያልነካች ኳስ አስተያየቱን ሊሰጥ ደግሞ “በእኔ እይታ ጐል አልገባችም፡፡ በተለያየ አንግል የሚቀርፁ ካሜራዎች የተለያዩ ምስሎችን ሊያመለክቱ ይችላሉ፡፡ የግብ መስመር ቴክኖሎጂ አስፈላጊነት እዚህ ላይ ነው፡፡›› ብሎ ተናግሯል፡፡ ሌላው የውዝግብ አጀንዳ ደግሞ የናይጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ ደጋፊዎች ድንጋይ ውርወራ ጉዳት እንደደረሰ በመግለፅ ፊፋ እርምጃ እንዲወስድ መክሰሱ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ለዚሁ ክስ እስከትናንት በስቲያ ምላሽ አልሰጠም፡፡
ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ 18 ደርሰዋል፤ 14 ይቀራሉ፡፡
ባለፈው ሰሞን በ20ኛው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን በመወከል የሚሳተፉ 5 ቡድኖች ለመለየት በተደረጉት የጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች በኋላ አልጀሪያ፣ ካሜሮን፣ አይቬሪኮስት፣ ናይጄሪያና ጋና በመልስ ጨዋታቸው ወደ ዓለም ዋንጫ የሚያልፉበትን የተሻለ ዕድል ይዘዋል፡፡ ከዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ትንቅንቆች ኢትዮጵያ በሜዳዋ ናይጀሪያ አስተናግዳ 2ለ1 ከተሸነፈችበት ጨዋታ ባሻገር፣ አይቬሪኮስት ሴኔጋልን 3ለ1፤ ቡርኪናፋሶ አልጀሪያን 3ለ2 እንዲሁም ጋና ግብጽን 6ለ1 በሆነ ውጤት በየሜዳቸው አሸንፈዋል፡፡ ቱኒዚያ ደግሞ በሜዳዋ ካሜሮንን አስተናግዳ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ከወር በኋላ በሚደረጉት የመልስ ጨዋታዎች ከ4 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 19ኛው ዓለም ዋንጫ አፍሪካን የወከሉት ቡድኖች በብራዚሉ 20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ውክልናቸውን እንደሚደግሙ ግምት አሳድሯል፡፡

እነሱም አልጀሪያ፣ ካሜሮን፣ አይቬሪኮስት፣ ናይጄሪያና ጋና ናቸው። ከአፍሪካ ባሻገር ባለፈው ሳምንት በመላው ዓለም ከተካሄዱ ሌሎች የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮች በኋላ ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ ያለፉት ብሔራዊ ቡድኖች ብዛት 18 ደርሷል፡፡ ከ1 ወር በኋላ በቀሩት የ14 ብሔራዊ ቡድን ኮታዎች ተሳትፏቸውን የሚያረጋግጡ ብሄራዊ ቡድኖች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ከአውሮፓ ዞን ያለፉት 9 አገራት ሆላንድ፣ ጣልያን፣ ቤልጅየም፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ስፔን፣ እንግሊዝ፣ ሩስያ እና ቦስኒያ ሄርዞጐቪና ናቸው፡፡ ለአውሮፓ በሚቀሩት የአራት ቡድኖች ኮታዎች ፖርቱጋል፣ ክሮሽያ፣ ዩክሬን፣ ግሪክ፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ሮማንያ እና አይስላንድ በጥሎ ማለፍ የመጨረሻ ትንቅንቅ የሚደረግላቸውን የጨዋታ ድልድል በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ከኤሽያ ዞን ለዓለም ዋንጫው ማለፋቸውን ያረጋገጡት አራት አገራት ጃፓን፣ አውስትራሊያ፣ ኢራንና ደቡብ ኮርያ ናቸው፡፡ በሚቀረው የአንድ ብሔራዊ ቡድን ኮታ ከኤሽያ ዞን የምትወከለው ዮርዳኖስ እና የደቡብ አሜሪካ ተወካይ የሆነችው ኡራጋይ በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ይገናኛሉ፡፡ ከደቡብ አሜሪካ ዞን አዘጋጇን ብራዚል ጨምሮ አርጀንቲና ፣ ኮሎምቢያ ቺሊና ኢኳዶር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ዞን አሜሪካ፣ ኮስታሪካና ሆንዱራስ ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ በቀረው የአንድ ብሔራዊ ቡድን ኮታ ከዚሁ ዞን የምትወከለው ሜክሲኮና ከኦሽንያ የምትወከለው ኒውዝላንድ በጥሎ ማለፍ ይተናነቁበታል፡፡

አዲሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ
አቶ ጁነዲን ባሻህ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለሚቀጥሉት አራት አመታት በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት ዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ ከማድረጋቸው ሶስት ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ነበር፡፡ የድሬደዋ ከተማ መስተዳድርን በመወከል በምርጫው ተወዳድረው ድምፅ ከሰጡት 106 የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የ55ቱን ድምፅ በማግኘት አዲሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡ አቶ ጁነዲን ላለፉት 20 ዓመታት ከስፖርቱ ጋር ትስስር ነበራቸው፡፡ በተለይም የሐረር ቢራ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው በሰሩበት ወቅት ክለቡን ለፕሪሚየር ሊግ አብቅተውታል፡፡ ስለዓላማቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳደር ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማስፈን እሰራለሁ ብለዋል፡፡

በመላው አገሪቱ እግር ኳስን በተሻለ ደረጃ ለማስፋፋት ተስፋ እንደሚያደርጉ በመግለፅ፤ ስፖርቱን በተረጋጋ የለውጥ ሂደትና በዘመናዊ መዋቅር ለመምራት እንደሚፈልጉና በወጣት ፕሮጀክቶች ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል፡፡ በንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች ከፍተኛልምድ ያላቸው አቶ ጁነዲን ባሻህ እግር ኳስ ከዝንባሌ ባሻገር ትልቅ ንግድ እንደሚሆን በተግባር የማሳየት ፍላጎት እንዳላቸው ያስገነዝባሉ፡፡ ክለቦች የገቢ ምንጮቻቸውን በማስፋት ሊለወጡ በሚችሉበት የእድገት አቅጣጫ ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁ ናቸው፡፡ አቶ ጁነዲን ባሻህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው በተሾሙበት እለት ከዚህ በታች የቀረበውን አጭር ቃለምምልስ ከስፖርት አድማስ ጋር አድርገው ነበር፡፡
በሃላፊነት ሳምንት እንኳን ሳይሞላዎት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ የጥሎ ማለፍ ትንቅንቁን በሜዳው ይጀምራል፡፡ ሁኔታውን እንዴት ይመለከቱታል?
በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአለም ዋንጫ ባያልፍ ምን ይመጣ ይሆን የሚለው ያስጨንቀኛል። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ውጤት እንዲመጣ ከመጓጓት ነው። አሁን ደግሞ ሃላፊነት ላይ እንደተቀመጠ ሰው በዚህ ሽግግር የተጨናነቁ ነገሮች እንዳይመጡ ፍላጐቴ ነው፡፡ ቢቻል ከቀድሞው አመራር ጋር በቦታው ተገኝተን ቡድናችንን በጋራ ብናይ፣ በሰከነ ሁኔታ ተጨዋቾቻችን እንዲጫወቱ ፤ ተመልካቾችም ድጋፍ እንዲሰጡ አስባለሁ፡፡ በአጠቃላይ መልካም ነገር እመኛለሁ። ዋሊያዎቹ መልካም ነገር እያስመዘገቡ ነው የመጡት፡፡ አሁንም የምንጠበቀው ይህን ነው፡፡ የአመራር መለዋወጥ ከውጤቱ ጋር ብዙም የሚነካካ ነገር የለውም፡፡
ዋልያዎቹ ለዓለም ዋንጫ ቢያልፉ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያመጣል፡፡ እርስዎ ምን ይጠብቃሉ?
በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ተመልካች ስታድዬም እየገባ በእግር ኳስ ውጤት እያዘነ የወጣበት ዓመታት ብዙ ናቸው፡፡ ለዚህ ተመልካችና ለዚህ ህዝብ ብሄራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ቢያልፍ መቼም ለሁላችን የሚፈጠረው ደስታ መጠን ያለው አይመስለኝም። እንግዲህ ይህን የሚፈጽሙት ሜዳ የሚገቡት ተጫዋቾች እና የብሄራዊ ቡድኑ አጠቃላይ አባላት ናቸው፡፡ አደራውን ለተጨዋቾችና ለአሠልጣኝ ነው የምሰጠው፡፡ በአጠቃላይ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ በአፍሪካ እና ዓለም ደረጃ ጥሩ ገጽታ ይፈጥርልናል ብዬ ነው የማስበው፡፡
ድሮ ኳስ ስንት ቁጥር ለብሰው ነበር የሚጫወቱት?
በተማሪነቴ ስምንት ቁጥር ለብሼ ነበር የምጫወተው፡፡
ከውጭ ኳስ የማን ጨዋታ ደስ ይልዎታል?
የእንግሊዝ እና የስፔን ክለቦችን በብዛት እከታተላለሁ፡፡
የሚያደንቁት ተጫዋችስ?
በፊት ለአርሰናል ይጫወት የነበረው ሄነሪ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የሮናልዶና የሜሲ አጨዋወት በጣም ይስበኛል፡፡
ዋልያ የሚለው ቅፅል ስም ተስማምትዎታል?
በአገራችን ያለ ብርቅዬ እንስሳ ስለሆነ አዎ ለአለም ላይ የቱሪዝም ሃብታችንን ማስተዋወቅ ነው፡፡
የድሬድዋ ሰው ኳስን የሚወደው በምን የተነሳ ነው?
ድሬዳዋ ሜዳው ለጥ ያለ ነው፡፡ አሸዋ ነው፡፡ ብትወድቅም ብትንከባለልም፡፡ የሚወስደን ጐርፉ ብቻ አይደለም፡፡ አሸዋውም ላይ ኳሱም አለ፡፡ ህዝቡ በተፈጥሮው ለፊልም፣ ለቲያትር በአጠቃላይ ለጥበብ የተሰጠ ነው፡፡ ባህሉ ሰውን የሚያቀራረብ ነው፡፡ ድሬደዋ ለጅቡቲ ካላት ቅርበት በብዙ መልኩ የአለምአቀፍ ዕሳቤ እና ስልጣኔ አላት፡፡ ስፖርት ደግሞ ስልጣኔ ነው፡፡ በስፖርቱ መስክ የሚመዘገብ እድገት እና ለውጥ የስልጣኔ መገለጫም ይሆናል፡፡
ወደ ስፖርት ከገቡ ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል። በእነዚህ ጊዜያት ብዙ አመራሮች በፌደሬሽኑ አስተዳደር ተቀያይረዋል፡፡ እርስዎ የፌደሬሽን አመራር እሆናለሁ ብለው አስበውት ያውቃሉ?
ስፖርት ያረካኝ ነበር፡፡ ስፖርትን ኳስ በመምታት አይደለም የማስበው ከዛ በላይ ነው፡፡ ክለብ ስናቋቁምም ወጣቱ የሚያተኩርበት ነገር እንዲያገኝ ከሚል ነው፡፡ አንዳንዴ ያሰብክበት ብቻ አይደለም የምትውለው ፈጣሪ የትም አውሎ ያስገባኝ የምትልበት ጊዜ አለ፡፡

 

               እ.ኤ.አ 2013 ዓ/ም ወደ ማለቂያው እየተዳረሰ ነው፡፡ የዛሬ አስራ ሶስት አመት ማለትም እ.ኤ.አ በ2000/ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሀገራትን አስተባብሮ አለም አቀፍ የልማት ግቦችን መንደፉ ይታወሳል፡፡ 189/ የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገራት በጋራ ወደ ስምንት የሚደርሱ የልማት ግቦችን ከነበሩበት ደረጃ እስከ 2015/ዓ/ም መሻሻል እንዲያሳዩ ሲታቀድ በዚ ህም ወደ 23/ የሚደርሱ አለም አቀፍ ድርጅቶች ግቡ እንዲሳካ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ በት መድረክ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ስምንት የልማት ግቦች ውስጥ የተወሰኑት ከጤና ጋር የተ ያያዙ ናቸው፡፡ በቅርቡ በተሰማው ዜና የልማት ግቦቹን ከማሳካት አንጻር በተለይም በአፍሪካ ወደ አምስት ሀገሮች በአብዛኛው የተሳካላቸው መሆኑ እና ኢትዮጵያ እንዲያውም ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘች ተገልጾአል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም ከሕጻናት ሞት ጋር የተያያ ዘው የልማት ግብ የተሳካ መሆኑ ቀደም ብሎ ተገልጾአል፡፡ ነገር ግን ከእናቶች ጤና ጋር በተያዘ የታለመወ ግብ እስከአሁን ድረስ ከተጠበቀበት ያልደረሰ በመሆኑ ወደፊት በተወሰነለት ጊዜ ከግቡ መድረስ ይችላልን? ከሚል ለሚሰነዘሩ ጥያቄዎች በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ቸውን ሰጥተዋል፡፡
                                              -----///------
ጥ/ የምእተ አመቱ የልማት ግብ ከጤና አኩዋያ ከምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?
መ/ ከምእተ አመቱ የልማት ግቦች መካከል ቁጥር 4 ፣5 እና 6 / በቀጥታ ከጤና ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በተራ ቁጥር 4/ የተመዘገበው የህጻናትን ሞት መቀነስ የሚባለውን በተባበሩት መንግስታት እንደተረጋገጠው ኢትዮጵያ በ2012ዓ/ም አሳክታለች፡፡ በ6ኛው ተራ ቁጥር የተመዘገበው የልማት ግብ ተላላፊ በሽታዎችን ፣ ሳምባን ፣ወባንና ኤችአይቪን መቀነስ ሲሆን ይህንንም ኢትዮጵያ በልማት ግቡ እቅድ መሰረት ካሳኩት አገራት መካከል ተመድባለች፡፡ ነገር ግን ትልቁ ችግር በተራ ቁጥር 5/ የተመዘገበው ከእናቶች ጤና ጋር የተያያዘው የልማት ግብ ምንም እንኩዋን እስከአሁንም ብዙ የተሰሩ ስራዎች ቢኖሩም ከተፈለገው ደረጃ ግን አልተደረሰም፡፡ ስለዚህም ክፍተት ስለሚታይ ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን ግልጽ ነው፡፡
ጥ/ የምእተ አመቱን ቁጥር 5 /የልማት ግብ ለማሳካት በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ምን በመደረግ ላይ ነው?
መ/ የእናቶች ሞት ከሚመጣባቸው ምክንያቶች መካከል ሶስቱ መዘግየቶች የሚባሉት ትልቅ ችግር እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
የመጀመሪያው መዘግየት እናቶች ከመውለዳቸውም በፊት ሆነ ከወለዱ በሁዋላ ወደ ጤና ተቋም ሄደው ከሕክምና ባለሙያ ጋር ምክር አለማድረጋቸው እና በወሊድ ጊዜ በጤና ተቋም ሄደው አለመው ለዳቸው ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የቤተሰብ የልማድ፣ የባህል የመሳሰለው የአመለካከት ችግር ወደጤና ተቋም ሄደው እንዳይወልዱ ማድረግ አንዱ ተጠቃሽ ችግር ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በጤና ጥበቃ ሚኒስር የጤና የልማት ሰራዊት የሚባል በአገር ደረጃ ኃይል የተደራጀ ሲሆን አንድ ለአምስት በሆነ አሰራር እናቶችን፣ ቤተሰቡን የሚመለ ከተውን ሁሉ በሚያዳርስ መልክ እንዲሁም የልማት ቡድን በማዋቀር ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ የዚህ ስራ ዋና አላማው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም እናቶችን በማነቃቃት የአመለካከትን ችግር ለመለወጥ ነው፡፡ ይህም በተግባር እየተተረጎመ ነው፡፡
ሁለተኛው መዘግየት የሚባለው እናቶች ወደ ሆስፒታል መሄድ እየፈለጉ በትራንስፖርት ችግር ምክንያት መቅረታቸው ነው፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስር ይህንን ችግር ለመፍታት በሁለት መንገድ እየተከታተለው ነው፡፡
እናቶችን ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ እስከዋና መንገድ ድረስ ማለትም መኪና ሊገባበት እስከሚችለው መንገድ ድረስ ባህላዊ አምቡላንሶችን በአካባቢው ቁሳቁስ እንዲዘጋጁ በማድረግ በአካባቢው በሚኖሩ ወጣቶች አማካኝነት በማጉዋጉዋዝ ላይ ስንሆን በዚህም ትልቅ ለውጥ እየታየ ነው፡፡
እናቶች በባህላዊ አምቡላንስ አማካኝነት ወደ ዋና መንገድ ከደረሱ በሁዋላ ደግሞ አምቡላንስ በማቅረብ ወደጤና ተቋም እንዲደርሱ እየተደረገ ነው፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስር በወረዳ ደረጃ አንድ አምቡላንስ ... ባጠቃላይም ወደ ስምንት መቶ አምቡላንሶችን አሰማርቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። የአንቡላንሶቹን አቅርቦት በተለይም ሰፋፊ ወረዳዎች ላይ ቁጥራ ቸውን ለመጨመር እንዲቻል አሁንም ወደ አራት መቶ አምቡላንሶች የተ ዘጋጁ ሲሆን በቅርቡ ለተገልጋዩ ይቀርባሉ። ስለዚህ ሁለተኛውን መዘግየት በዚህ መንገድ ለመቅረፍ ስራ በመሰራት ላይ ነው፡፡
ሶስተኛው መዘግየት የሚባለው እናቶች ጤና ተቋም ከደረሱ በሁዋላ በጤና ተቋም አማካኝነት የሚደርሱባቸው ችግሮች ናቸው፡፡ ይኼውም የሚገለጸው ፡-
የጤና ተቋማቱ ለእናቶች በቅርበት አለመኖራቸው፣
እናቶች የሚፈልጉትን አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ አለማቅረብ፣
የሚሉት በሶስተኛው መዘግየት የሚጠቀሱ ናቸው። ይህንንም ለመቅረፍ በኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎት ከ3200 ሶስት ሺህ ሁለት መቶ በላይ ጤና ጣቢያ ዎች እና ከ 17000 አስራ ሰባት ሺህ በላይ ጤና ኬላዎች እንዲሁም 126 አንድ መቶ ሀያ ስድስት የገጠር ሆስፒታል በስራላይ ያሉ ሲሆን በተጨማሪም 150 አንድ መቶ ሀምሳ በዚህ አመት ወደስራ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ ያለውን ሽፋን ከ95% ማድረስ ተችሎአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎችን በመድሀኒትና አቅርቦት ፈንድ ተቋም ለማቅረብ ተችሎአል፡፡
ጥ/ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በከፍተኛ ሁኔታ መሰራት ይገባዋል የሚባለው የትኛው ነው?
መ/ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በከፍተኛ ሁኔታ መሰራት አለበት የሚባለው የጤና ባለሙያዎችን በሚመለከት ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎች ሲባልም ሐኪሞች ፣ነርሶች ፣ሚድ ዋይፎች ፣ኼልዝ ኦፊሰሮች ፣የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ በሕክምናው ዘርፍ የተወሰኑ አመታትን ከሰሩ በሁዋላ ለማስተማር ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም የቅበላ አቅማቸውን በመጨመር ትምህርቱን በማስተማር ላይ በመሆናቸው አበረታች ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ነገር ግን አንድን ጠቅላላ ሐኪም የጽንስና ማህጸን ሐኪም ለማድረግ አራት አመት ይፈጃል፡፡

ስለሆነም ለምእተአመቱ የልማት ግብ ውጤታማነት ለመድረስ አዳጋች ስለሚሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስር እንደ ኢሶግ ካሉ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ባለሙያዎች አቅማቸውን እንዲያደረጁ በማድረግ ላይ ነው፡፡ በዚህ አሰራርም የጤና መኮንኖችን ሶስት አመት በማሰልጠን በአፋጣኝ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ስራ ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ ገጠር ላሉ ጤና ተቋማት ለእያንዳንዱ ሁለት ሁለት ለማዳረስ በማሰብ አንድሺህ ባለሙ ያዎችን ለማሰልጠን ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለት መቶ የሚሆ ኑት ስልጠናቸውን ጨርሰው ወደ የሆስፒታሉ የተመደቡ ሲሆን ከዚያም በላይ ይጠበ ቃል፡፡ አንድ የጤና ባለሙያ ቀዶ ሕክምና በሚያካሂድበት ጊዜ ስራውን ብቻውን ስለማይሰራው አዋላጅ ነርሶች እንዲሁም ሰመመን ሰጪዎችም አብ ረው ስልጠናውን እየወሰዱ ነው፡፡ ስለዚህ ሙያው እጅ ለእጅ በመያያዝ መልክ ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከጤና ባለሙያ ማፍራት ድረስ በመሰራት ላይ በመሆኑ የእና ቶችን ሞት ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት በምእተ አመቱ የልማት ግብ በተለይም በተራ ቁጥር 5/የተመዘገበው የእናቶች ሞትን መቀነስ በሚመለከት በሰጡት አስተያየት፡-
“… በእርግጥ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ነገር ግን የሚሰሩት ስራዎች በአፋጣኝ ውጤት የሚገኝባቸው ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የተሰሩ ስራዎች ነገ ተነገወዲያ ጥሩ ውጤት እንደሚያሳዩ እሙን ነው፡፡ የእናቶችን ሞት ከሶስቱ መዘግየቶች ጋር ብቻ አያ ያዘን የምእተ አመቱን ግብ አልተሳካም ብለን መደምደም የለብንም፡፡ ምክንያቱም እናቶ ችን ከማዳን አንጻር ሌሎች ብዙ የሚጠቀሱ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ኤችአይቪ ኤይድስ ለእናቶች ሞት ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ምክንያት ሲሆን በዚህ ላይ ብዙ ጥሩ ነገር ተሰ ርቶአል፡፡ ወባ ለእናቶች ሞት ምክንያት እንደሚሆን እርግጥ ሲሆን የወባ መቀነስ ለእና ቶች ጤንነት መሻሻል አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በኩል ከፍተኛ ስራ እየተሰራ በመሆኑ ወደ አምስት እጥፍ ያህል ሽፋኑ ጨምሮአል፡፡ ይህም የእናቶችን ጤና ለማሻሻል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ምንም አያጠያይቅም፡፡ የተባበሩት መንግስታት ጥናት እንደሚያሳየው የእናቶችን ሞት በመቀነስ ረገድ በኢት ዮጵያ ባለፉት ሀያ አመት ውስጥ በየአመቱ 4.9 ኀ ያህል እየቀነሰ መሆኑን ያሳያል፡፡ይህ ውጤት የሚያሳየን የል ማት ግቡን በጊዜው ልናሳካ ባንችልም እንኩዋን ጥሩ ውጤት መሆኑን መገንዘብ ይገባ ናል...ብለዋል፡፡”

Published in ላንተና ላንቺ

ለልማት የሚከፈለው መስዋዕትነት በ“ደብል ዲጂት” መቀነስ አለበት!
ልማትና ትዕግስት ያላቸው ቁርኝት ዘንድሮ ገባኝ!
እኔ የምለው … ባለፈው እሁድ ብሄራዊ ቡድናችን ብሔራዊ ኩራት አጐናፀፈን አይደል! (የልማት ውጤት እኮ ነው!) እውነቴን ነው የምላችሁ… ዋልያዎቹ ብርቅዬነታቸውን ለዓለም አሳይተዋል። በቴክኒክ ችግር 2ለ1 በሆነ ውጤት ቢሸነፍም እንዳሸነፈ እንቆጥረዋለን፡፡ የደጋፊውንም የጨዋነት ብቃት ሳናደንቅ አናልፍም፡፡ አንዳንድ ደጋፊዎች ግን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የ “ማሪዋና” ቅጠል የታተመበት ባንዲራ ጭንቅላታቸው ላይ ሸብ አድርገው ታይተዋል-በኢቴቪ መስኮት ሳይቀር፡፡ (ይሄኔ ነው መሸሽ) አንዳንዶች ምን ቢሉ ጥሩ ነው? የአባባ ጃንሆይ ባንዲራ (የሞአንበሳ ምስል ያለበት) ማረን ብለዋል (ማስጠየቁ ባይቀርም) አሁንም ከስቴዲየም ወጥተን ፓርላማ እንግባ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት በአዲሱ ፕሬዚዳንት ንግግር ላይ ለፓርላማ የሰጡትን ማብራሪያ ተከታትላችኋል? ንዴት የማይነካቸው ጠ/ሚኒስትር ሰጥቶናል እንጂ በፓርላማ የመድረክ ተወካይ ስንት ጭርጭርር….የሚያደርግ ውንጀላ ሰንዝረዋል - በጠ/ሚኒስትሩ ላይ ሳይሆን በመንግስትና በኢህአዴግ ላይ፡፡ ዳያስፖራው በ40/60 የመንግስት ቤቶች ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆን የተደረገው፣ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ለመሰብሰብና ዳያስፖራውን በአባልነት ለመያዝ ነው ሲሉ አቶ ግርማ የወንጀሉ ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩ ግን ተረጋግተው ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኢህአዴግ ከዳያስፖራው ድምፅ (የምርጫ ማለታቸው ነው) አያገኝም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከዳያስፖራ የገንዘብ ድጋፍ ተቀብሎ እንደማያውቅም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ (ኢህአዴግ እኮ ቀጭን ጌታ ነው!)

ይሄ ደግሞ እውነት መሆኑን ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ እንዴ 7 ሚ. አባላት ያቀፈ ግዙፍ ፓርቲ ለምን ብሎ ከዳያስፖራ ገንዘብ ይለምናል፡፡ (በደህና ቀን ተቃዋሚ ፓርቲ ከመሆን ወጥቷል!) በዚያ ላይ በሽ የቢዝነስ ተቋማት አሉት (“ኢንዶውመንት” ነው የሚላቸው?) በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ራሱን “አውራ ፓርቲ” ቢልም እኮ ያምርበታል፡፡ ትልቅ ሥልጣን (Power) ብቻ ሳይሆን ትልቅ ካፒታልም ያለው ፓርቲ እኮ ነው! እኔ ተቃዋሚ ፓርቲ ብሆን ኖሮ “ህልምህ ምንድነው? ስባል ምን እንደምል ታውቃላችሁ? “ህልሜ ኢህአዴግን መሆን ነው!” ባይናገሩትም እኮ የሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህልም ይሄው ነው፡፡ “ወፈ ሰማይ አባላት” ያሉት ገዢ ፓርቲ መሆን! ወዳጆቼ… “ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ማድረግ” ምናምን… የሚለው የተበላ ዕቁብ ነው!!
በ2000 ዓ.ም የኢህአዴግ ካፒታል ከ1200ሚሊዮን ብር በላይ ነበር አሉ፡፡ (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!) እኔ የምላችሁ … ከአነስተኛና ጥቃቅን የብድር ተቋማት፣ ገንዘብ ተበድረው ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡ ወጣቶች እንዳሉ ሰምታችኋል? የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ፓርላማ ውስጥ ሲናገሩ ሰምቼ እኮ ነው፡፡
ለነገሩ ጠ/ሚኒስትሩም ቢሆኑ ለማስተባበል አልሞከሩም፡፡ “ከስንዴ መሃል እንዳክርዳድ አይጠፋም” ዓይነት መልስ ነው የሰጡት፡፡ መፍትሄውም ስንዴውን ሁሉ መድፋት ሳይሆን እንክርዳዱን ለቅሞ ማውጣት ነው ብለዋል - የተከበሩ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፡፡
በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ተቃዋሚዎችና መንግስት ዓይን ያወጣ የእርስ በርስ መፈራረጅ አቁመው፣ የርዕዮተ ዓለም ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሚያግባባቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት አለባቸው ሲሉም አቋማቸውን ገልፀው ነበር (የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ምክር ትዝ አለኝ!) ጠ/ሚኒስትሩ ግን ይሄ የተዋጠላቸው አይመስሉም። በእርግጥ “የተቃዋሚዎች መኖር ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለገዢው ፓርቲም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል” በማለት ነው መልስ መስጠት የጀመሩት፡፡ ከዚያ ግን አመረሩ (ፊታቸው ላይ ምሬት ባይታይም!) “ሌት ተቀን የጐዳና ላይ ነውጥ አድርጌ መንግስት እለውጣለሁ” ከሚል ተቃዋሚ ጋር እንዴት ነው በጋራ መስራት የምንችለው?” በማለት ምላሽ ሰጡ፤ ጠ/ሚኒስትሩ። እኔ የምላችሁ ግን… “ነውጥ” ከ97ቱ ምርጫ ጋር “ታሪክ” አልሆነም እንዴ? እኔ እኮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቃዋሚዎች የሚያደርጉት ሰላማዊ ሰልፍ፤ ህጋዊና ሰላማዊ ይመስለኝ ነበር። ደግሞም አይፈረድብኝም … ህጋዊ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ አላቸው፡፡ ፖሊስ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡ እንዴት “ነውጠኞች” ብዬ ልጠርጥር?
መንግስት ባለሃብቱን ሁሉ “ኪራይ ሰብሳቢ” ይላል በሚል ለቀረበው ውንጀላ መልስ የሰጡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚለውን ቃል በትክክል ካለመረዳት የመጣ ስህተት ነው ብለዋል- በሰሞኑ የፓርላማ ውይይት፡፡ በ”ነውጥ” ጉዳይ ላይም ብዥታ (የኢህአዴግን ቋንቋ ተውሼ ነው!) ያለ ይመስለኛል፡፡
እናላችሁ … በሰላማዊ ሰልፍና በነውጥ መካከል ስላለው ልዩነት ጥልቅ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ዎርክሾፕ ነገር ያስፈልገናል፡፡ (ለእኛም፣ ለኢህአዴግም፣ ለተቃዋሚም)
በቀደም በፓርላማ ጠ/ሚኒስትሩ፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለ10 ተከታታይ ዓመት በሁለት ዲጂት ማደጉን ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ (ኒዮሊበራሎችም በግዳቸው አምነዋል!) አሁን የእኔ ጥያቄ ምን መሰላችሁ? የአገሪቱ ዲሞክራሲ ማደግና መውደቁን የሚነግረን ማነው? የሚል ነው፡፡ (በዲጂት ማለቴ ነው!) ከምሬ ነው… ዲሞክራሲያችን በስንት ዲጂት እንዳደገ እንዲነገረን እንፈልጋለን። (እንደኢኮኖሚው ባለሁለት ዲጂት አስመዝግቦ ይሆናል እኮ!) ነገሩን እኛ ሳናውቀው ቀርተን እኮ አይደለም፡፡ ለወዳጅም ለጠላትም ግን በፐርሰንት ተሰልቶ ሲነገር ደስ ይላል። (ዲሞክራሲ በፐርሰንት ይለካል እንዴ?)
መቼም ጉዳችን አያልቅም አይደል? የመብራት፣ የውሃ፣ የኔትዎርክ፣ የታክሲ መጥፋት ወዘተ… አንሶን ሰሞኑን ደግሞ የዳቦ እጥረት ተከስቷል - በስንዴ መጥፋት፡፡ እናላችሁ… ሌላ የዳቦ ሰልፍ እንዳይጀመር ክፉኛ ሰግቻለሁ፡፡ (እንደታክሲው!)
Daily Express የተባለው ጋዜጣ April 17 ቀን 1933 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ፤ በሶቭየት ህብረት በአንድ አርብ ቀን ብቻ 7ሺ ሩሲያውያን ለዳቦ ተሰልፈው እንደነበር ጽፏል፡፡ (ሰልፍና ሶሻሊዝም ተለያይተው አያውቁም!) እናላችሁ… ከእንዲህ ዓይነቱ መዓት እንዲሰውረን ሱባኤ መግባት ሳይኖርብን አይቀርም። (ሱባኤ ለመግባት የግድ 7ሺ ሰው ለዳቦ መሰለፍ አለበት እንዴ?)
ባለፈው ሳምንት የገጠመኝን ደግሞ ላውጋችሁ፡፡ እንደአጋጣሚ ካዛንቺስ አካባቢ መብራት ስላልጠፋ (አንዲት ማታ እኮ ነው!) ኢቴቪ በትራንስፖርት እጥረት ዙሪያ የሰራውን ዘገባ እየኮመኮምኩ ነበር። መፍትሔ ይመጣል የሚል ተስፋ አድሮብኝ እንዳይመስላችሁ፡፡ ሥራ ከምፈታ ብዬ ነው፡፡ የዛን ዕለት ማታና አንድ ሌላ ቀን ሁለት የካድሬ ቅላፄ ያላቸው የታክሲ ተራ አስከባሪዎች የሰጡት ድፍረት የተሞላበት አስተያየት ግርም ብሎኛል፡፡ ሁለቱም ሴቶች ናቸው፡፡

ሁለቱም ከአፋቸው ነጠቅ ነጠቅ ያደርጋቸዋል፡፡ ሁለቱም እየተቆጡ ነው የሚናገሩት። ተራ የማስከበር ሥራ ሳይሆን የአዲስ አበባን ነዋሪ ሥነምግባር የማስተማር ሃላፊነት የተጣለባቸው ይመስላሉ፡፡ በስራ ሰዓት መግቢያና መውጪያ ላይ ስለሚፈጠረው የትራንስፖርት እጥረት ነበር የሚናገሩት፡፡ “ህዝቡ…ቅጥቅጦች ላይ አይሳፈርም…ሁሉም ቆሞ ሚኒባስ (ታክሲ) ነው የሚጠብቀው፤ ይሄ ተገቢ አይደለም” አሉ፡፡ ወቀሳቸው አላበቃም “ህብረተሰቡ ለምን ማልዶ ተነስቶ ወደ ስራው አይሄድም? ሁሉም 2 ሰዓት ስለሚመጣ እኮ ነው ችግር የሚፈጠረው” አሁንም በቁጣ! አንደኛዋ ይባስ ብላ፣ል ሰራተኛው ጠዋት አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ ስራ እንዲገባ፣ ማታም እንዲሁ ከስራው አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ እንዲወጣ በፓርላማ ያልፀደቀ መመሪያ አወጣችልን፡፡
ለታክሲዎች እያቆራረጡ መጫንና ለታሪፍ ጭማሪም ተጠያቂው ህብረተሰቡ ነው ስትል ደመደመች፡፡ (አዲስ አበቤ ፈረደበት!) “ህዝቡ ራሱ እኮ ነው፤ መብቱን አያስከብርም!” አለች - ብላ፡፡
ይሄኔ አንድ ነገር ተጠራጠርኩ፡፡ ተራ አስከባሪዋ “ፒፕሉ” ላይ ቂም ሳይኖራት አይቀርም፡፡ ወይም ደግሞ “ይሄን ህዝብ ውረጂበት!” ብሎ የላካት “የውጭ ኃይል” አለ - አልኩ ለራሴ፡፡ በኋላ ላይ “እንተዋወቃለን እንዴ?” ልላት ሁላ ዳድቶኝ ነበር -በአካል አጠገቤ ያለች መስላኝ፡፡ የምትናገረው በኢቴቪ መስኮት መሆኑ ትዝ ሲለኝ በራሴ ላይ ከት ብዬ ሳቅሁኝ፡፡ (በራስ መሳቅ ጤንነት ነው ተብሏል!)
አይገርምም…በትራንስፖርት እጥረት ጠዋት ማታ የምንሰቃየው አንሶ ቤታችን ድረስ በኢቴቪ በኩል እየመጡ እንዲሁ ሲሞልጩን! ወደዘገባው መቋጫ ላይ ጋዜጠኛው ያነጋገራቸው የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ትንሽ ይሻላሉ፡፡ ህብረተሰቡ ለልማት የከፈለውን መስዋዕትነትና ታጋሽነት አድንቀዋል፡፡ (ሃበሻ እኮ በትዕግስት አይታማም!) የትራንስፖርት ችግሩን በተመለከተ ግን አንዳችም የመፍትሔ ሃሳብ አልሰነዘሩም፡፡ “በትዕግስታችሁ ግፉበት!” ከማለት በቀር፡፡
በነገራችሁ ላይ ልማትና ትዕግስት ያላቸውን ተፈጥሮአዊ ቁርኝት በደንብ የተረዳሁት ዘንድሮ ነው፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ግን እዚህች መዲናችን ላይ ለልማት የሚከፈለው መስዋዕትነት ልኩን ያለፈ ይመስለኛል፡፡ (ግን መስዋዕትነት ያስፈልጋል እንዴ?) አያችሁ… አንዳንዱ መስዋዕትነት ለመንግስት ሹመኞች ስንፈት የምንከፍለው ነው። ሁሉም እየተነሳ ችግሩንና ድክመቱን በልማቱ ሲያሳብብ አያበግንም?
የሰለጠኑት አገራት እኮ እንኳን ለልማት ለጦርነት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመቀነስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሰው አልባ ተዋጊ ጄቶችን ለምን የፈጠሩ ይመስላችኋል? መስዋዕትነትን በ “ደብል ዲጂት” ለመቀነስ እኮ ነው! እኛም የልማት መስዋዕትነታችንን በ “ደብል ዲጂት” መቀነስ አለብን!! (ሞትን እኮ!)

መኪና በዱቤ እየሸጠ ነው
መኪኖችን ወደ ውጭ ለመላክና አዳዲስ ሞዴሎች ለማቅረብ አቅዷል
የሚያሰራው ባለ 5 ኮከብ ሆቴል
ዘንድሮ ይመረቃል

ባለሀብቶቹ ሦስት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የትራንስፖርትና የኮንስትራክሽን ዘርፉን በተሽከርካሪ አቅርቦት በመደገፍ፣ በሀገሪቱ ልማት የበኩላቸውን ሚና መጫወት ስለፈለጉ፣ በ1996 ዓ.ም በአራት ሚሊዮን ብር በላይአብ ኢንተርፕራይዝ ኃ.የተ.የግ.ማ አቋቋሙ፡፡ የድርጅቱን አወቃቀር በማሻሻል በ100 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ በላይአብ ሞተርስ ኃ.የተ.የግ.ማ አሳደጉት፡፡ በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ጠቅላላ ሀብት 230 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን በ10 ሠራተኞች ጀምሮ አሁን ከ200 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ግርማ ይናገራሉ፡፡
የድርጅቱ ዋነኛ ተግባር፣ የተለያዩ የመኪና አካላትን ከውጭ አገር በማምጣት የተለያየ መጠን ያላቸው መኪኖችን መገጣጠም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ፋዋ ቤላ ሴዳን (FAW Vela Seden) የተባለች የቤት አውቶሞቢል፣ የኒሳን ሞተር የተገጠመለት ባለ ሁለት ጋቢናና 3.2 ሲሲ የፈረስ ጉልበት ያለው ፒክ አፕና ኦቲንግ ስቴሽን ዋገን (ሁለቱም የመስክ መኪና) በመገጣጠም በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እንደሚያቀርብ ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል። በተጨማሪም 16 ሜትር ኩብ የመጫን አቅም ያላቸው ፎቶን ሲኖ ትራክ ገልባጭና ከ15 እስከ 45 ኩንታል መሸከም የሚችሉ የጭነት ተሽከርካሪዎችን እያስመጣ እንደሚሸጥ ተናግረዋል፡፡ “የሥራ ዕድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ በማዳን፣ ራዕዩን አሳክቷል” ይላሉ አቶ ፍቃዱ፡፡
በላይአብ ሞተርስ በአሁኑ ወቅት በአዳማ የመኪና መገጣጠሚያ፣ በአቃቂ ዋና መ/ቤትና ሾው ሩም አለው፡፡ በቃሊቲ ደግሞ ድርጅቱ ለሸጣቸውም ሆነ ከውጭ ለሚመጡ መኪኖች ሰርቪስና የጥገና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የመለዋወጫ ችግርም እንደሌለ የክፍሉ ኃላፊ ይናገራሉ፡፡
ባለሀብቶቹ መኪና ለመገጣጠም እንደወሰኑ በቀጥታ ወደ ሥራ አልገቡም፡፡ ከአዲስ አበባና ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ የምህንድናስና ክፍል መምህራን ጋር በመመካከር መገጣጠም ያለባቸው የመኪና ዓይነቶችን መለየታቸውን የመገጣጠሚያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ስነ ገልጿል፡፡ የመኪኖቹ ዓይነት ይመረጥ እንጂ ወዲያውኑ የሚያስፈልጉት ዕቃዎች መጥተው አልተገጣጠሙም፡፡ መጀመሪያ የተመረጡትን ዓይነት መኪኖች በማስመጣት ለአየር ንብረቱ፣ ለመልከዓምድሩ፣ … ተስማሚና ምቹ መሆናቸው ከታየ በኋላ ነው መገጣጠሙ የተጀመረው፡፡
“የሚገጣጠሙት መኪኖች አካላት ከቻይና የመጡ ቢሆንም ከጃፓን ጋር በሚሠሩ ኩባንያዎች የሚመረቱ በመሆኑ ጥራታቸው አስተማማኝ ነው። ለምሳሌ የቤት መኪናዎች ዕቃ የሚመጣው ከቲያንጂን ቶዮታ ኩባንያ ሲሆን ፒክአፑን ደግሞ ከኒሳን ጆንጆ ኩባንያ ነው” በማለት አቶ ቢኒያም ስለ መኪናዎቹ ጥራት ገልጿል፡፡
አሁን ግን የመስክ ፒክአፖቹን እንደ ቀድሞው ለመሸጥ ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የመንግሥት የሆነው ድርጅት ተመሳሳይ የመስክ መኪና መገጣጠም በመጀመሩ ነው። በፊት የመንግሥት ድርጅቶች የመስክ መኪና ለመግዛት ጨረታ ሲያወጡ፣ እየተጫረቱ ይሸጡ ነበር፡፡ አሁን ግን መንግሥታዊ የሆነው የቢሾፍቱ ኦቶሞቲቭ ኢንተርፕራይዝ ፒክአፖቹን ስለሚሠራ፣ የመንግሥት ድርጅቶች የሚገዙት ከዚያ ነው፡፡ ይህም ገበያቸውን አቀዝቅዞታል፡፡
“የቤት ኦቶሞቢሎቹ ሽያጭ ግን ከጠበቅነው በላይ ነው፡፡ የግለሰቦች የመግዛት አቅም እየተሻሻለ በመሆኑና መኪኖቹ በአንድ ሊትር 18 ኪ.ሜ በመጓዛቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ በጣም ተወደዋል። መንግሥት፣ ቤት ለሁሉም ሰው ለማዳረስ እንዳቀው ሁሉ፤ እኛ ደግሞ መኪና ለሁሉም ሰው ለማዳረስ የዱቤ ፕሮግራም አዘጋጅተን ብዙ ሰዎች ተጠቅመዋል፡፡ ሌሎችም በዕድሉ እንዲጠቀሙ በስፋት እየሠራን ነው” ብሏል አቶ ቢኒያም፡፡
የመኪና አካላት ብዙ ናቸው፡፡ ከውጭ አገር መጥተው እዚህ በትክክል መገጣጠማቸውን የሚጠራጠሩ ሰዎች አሉ፡፡ “በኮምፒዩተር በመታገዝ ከፍተኛ የጥራት ቁጥጥር ስለሚደረግ፣ በዚህ በኩል ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይግባችሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእኛ መኪና ገዝተው እየተጠቀሙ ያሉ ደንበኞቻችን እማኞች ናቸው” ይላሉ ሥራ አስኪያጁ በኩራት፡፡ ለመሆኑ እንዲህ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ያበቃቸው ምን ይሆን?
“አንድ መኪና ምን ያህል ዕቃዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ የታዘዙት ዕቃዎች ከአቅራቢው ድርጅት በትክክል መላካቸውን እናረጋግጣለን። በአንድ ጊዜ የሚመጣው የ36 መኪና ዕቃ ነው፡፡ ዕቃዎቹ ትክክለኛ መሆናቸውን፣ የዕቃዎቹን መጠን፣ ቁጥራቸውን፣ ለእያንዳንዱ መኪና ስንት ዕቃ እንደመጣ፣ በትክክል መግባታቸውን በኮምፒዩተር ተፈትሾ ይረጋገጣል፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ዕቃዎቹ በሚገጠሙበት መስመር ተደርድረው ይቀመጣሉ። የዚያ መስመር ሠራተኛ ሥራ ከመጀመሩ በፊት፣ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎች መኖራቸውን አረጋግጦ ነው ሥራ የሚጀምረው፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ዓይነት ቁጥጥር አለ፡፡ አንደኛው የመጣው ዕቃ ጥራት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዕቃው በትክክል መገጠሙን ይቆጣጠራል፡፡
“አንደኛው ክፍል ገጣጥሞ ከጨረሰ በኋላ በትክክል መግጠሙን ፈትሾና አረጋግጦ ነው ለቀጣዩ ክፍል የሚያስተላልፈው፡፡ ሁለተኛው ክፍልም የመጣለትን ዝም ብሎ አይቀበልም፤ በቀደመው ክፍል መገጠም ያለባቸው ዕቃዎች መኖራቸውን አረጋግጦ ነው የሚረከበው፡፡ እሱም በተራው ለሦስተኛው ክፍል ሥራው በትክክል መጠናቀቁን ፈትሾና አረጋግጦ ያስተላልፋል፡፡ ሦስተኛውም በተራው ሁለቱ ክፍሎች እንዳደረጉት ፈትሾና አጣርቶ ለቀጣዩ ክፍል ያስተላልፋል፡፡ በዚህ ዓይነት የሚሠሩ ሦስት ስቴሽኖች አሉ፡፡ በእያንዳንዱ ስር ደግሞ ሦስት ሦስት ሳብ ስቴሽኖች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ክፍሎች በትክክል መግጠማቸውን አረጋግጠው ካሳለፉ በኋላ የጥራት ቁጥጥር (Quality control) ክፍሉ ፍተሻ ያደርጋል። ስለዚህም ምንም ዓይነት ዕቃ ሳይገጠም አያልፍም፡፡ መዘለል ብቻ ሳይሆን የአገጣጠም ስህተት እንኳ ቢኖር፣ በየክፍሉ እርምት ይደረግበታል፡፡ ስለዚህ ሦስት ጊዜ በክፍሉ፣ ከክፍሉ ሲወጣና በኳሊቲ ኮንትሮል ቁጥጥርና ፍተሻ ይደረጋል፡፡
“የዚህ ዓይነት እጅግ በርካታ (የቀለም፣ የመሪ፣ የፍሬን፣ …) ፍተሻና ቁጥጥር በየክፍሎቹና በኳሊቲ ኮንትሮል ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ፣ መሪው ወደቀኝ ወይም ወደግራ የሚጐትት ከሆነ፣የሚፈተሽበት መሳሪያ እጅግ ዘመናዊ በመሆኑ፣ ስህተት ካለ አያሳልፍም - ቀይ ያበራል፡፡ ስህተቱ ሲስተካከል አረንጓዴ አብርቶ ያሳልፋል፡፡ ይህን ሁሉ ፍተሻና ቁጥጥር ካለፈ በኋላ ወደመጨረሻ ፍተሻ (ሬን ቴስት) ይገባል፡፡ መስተዋቶች፣ በሮች፣ … በትክክል ካልተገጠሙ፣ ውሃና አቧራ ሊያስገቡ ይችላሉ። ስለዚህ፣ መኪናው ከስርም ሆነ ከላይ ኃይለኛ ግፊት ባለው ውሃ ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህም ጊዜ ስህተት ከተገኘ እንደገና ወደ ኋላ ተመልሶ ስህተቱ ይታረማል። የመጨረሻ ምርመራ የሚሆነው መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት መሞከር ነው - ጭነት ጭኖና ሳይጭን፡፡ ለምሳሌ አምስት ሰዎች የምትጭነውን ትንሿን መኪና ብንወስድ፣ ሾፌሩ ብቻውን እየነዳ ሲሄድ ምንም ችግር ላይኖር ይችላል፡፡ ከዚያም አራት ሰዎች ጭኖ ይሄዳል። በዚህ ጊዜ የተለያዩ ድምፆች የሚያሰሙ ከሆነ፣ እንደገና ይስተካከላል፡፡ ስለዚህ፣ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ ድረስ ድርድር የሌለው የኳሊቲ ኮንትሮል ፍተሻና ቁጥጥር ስለሚደረግ የመኪኖቻችን የጥራት ደረጃ ከፍተኛ ነው” በማለት አቶ ቢኒያም አስረድቷል፡፡
በመገጣጠሚያው ውስጥ በአመራር ደረጃ ያሉ ሠራተኞች በኦቶሞቲቭና በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ ከቴክኒክና ሙያ የተመረቁ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ትጉህ ሠራተኞችን ወደ ቻይና ልኮ ያሠለጥናል፤ ከቻይና ባለሙያዎችን አስመጥቶም የሥራ ላይ ሥልጠና ይሰጣል፤ ጥሩ የሥራ ውጤት ያላቸውን ሠራተኞች በኮሚቴ ታይቶ ትምህርታቸውን እንዲያሻሽሉ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በሌሎች መገጣጠሚያዎች የሠሩ ልምድ ያላቸው ሠራተኞችም አሉ፡፡
መገጣጠሚያው፣ ግንባታውና የማሽን ተከላው ተጠናቆ ሥራ የጀመረው በመስከረም 2003 ዓ.ም ነው፡፡ በመገጣጠሚያው ውስጥ ብቻ የሚሠሩ 65 ሠራተኞች ሲኖሩ፣ የሕክምናና የትራንስፖርት አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ያኔ ካፒታሉ 60 ሚሊዮን ብር እንደነበር አቶ ቢኒያም ገልጿል፡፡
የከባድ መኪና መገጣጠሚያ መስመር የተጠናቀቀ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ግን መገጣጠም አልጀመረም፡፡ ምን ዓይነት ተሽከርካሪ እንገጣጥም? ስንት ሰው የመጫን አቅም ያለው (28 ሰው፣ 48 ሰው፣ 65 ሰው፣ …) አውቶቡስ እንሥራ በማለት እያጠኑ ነው፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ፍቃዱም ሆኑ አቶ ቢኒያም፣ ጉምሩክ የሚያስከፍላቸው ቀረጥ ከፍተኛ በመሆኑ የሚያበረታታ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ አቶ ቢኒያም የቀረጥ ማበረታቻው አነስተኛ ነው ይላል። “ማንኛውም መኪና አስመጪ ከሚከፍለው ያላነሰ ነው የምንጠየቀው፡፡ እኛ እዚህ ለዜጐች የሥራ ዕድል ፈጥረን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር አምጥተን፣ እሴት ጨምረን መሸጣችን፣ ምንም አልታሰበም፡፡ መርካቶ ሱቅ ተከራይቶ መኪና እያመጣ ከሚሸጠው እኩል ነው የምንቀረጠው፡፡ ይህ አሠራር ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል ስለማያስችለን የቀረጥ አስተያየት እንዲደረግልን ጥያቄ አቅርበን እየተጠባበቅን ነው” ብሏል፡፡
በጉምሩክ አካባቢ እስካሁን ምንም ችግር አልገጠመንም ነበር ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በቅርቡ በወጡ አዋጆች ላይ የአተረጓጐምና የአፈጻጸም (ደብል ታክሴሽን) ችግር መኖሩን ገልፀዋል፡፡
“ይኼ አሠራር ችግር አለው ብለን አመልክተናል፤ በጐ ምላሽም እንደምናገኝ እንጠብቃለን፡፡ ነገር ግን አሠራሩ አይሻሻልም፤ ይኸው ነው ከተባለ፣ መኪና አገር ውስጥ ከመገጣጠም ይልቅ ከውጭ አምጥቶ የሚከፈለው ታክስ ይመረጣል፡፡ ደብል ታክሴሽን የሚፀና ከሆነ፣ በፊት የሚከፈለውን እጥፍ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ኢንዱስትሪውንም ይገድላል” ብለዋል፡፡ ሌላው አቶ ፍቃዱ ያነሱት ችግር፣ ከፋይናንስ ተቋማት በሚፈለገው መጠን የገንዘብ ብድር ከማግኘት ነው፡፡
በላይአብ ሞተርስ፣ በቀን 18 መኪና የመገጣጠም አቅም አለው፡፡ አሁን ግን በሙሉ አቅሙ ማምረት ደረጃ አልደረሰም፡፡ የመስክ ፒክአፑን ለመገጣጠም 2፡30፣ የቤት መኪናዋን ለመገጣጠም ደግሞ 2፡00 ይወስድበታል፡፡ መኪኖቹን የሚገጣጥሙት መጋዘን ባለ ዕቃ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ሽያጩ እጅ በእጅ ነው። ገዢው ክፍያውን ሲፈጽም ወዲያውኑ መኪናውን ይረከባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሽያጭ በርክቶ ከመጋዘን ዕቃ ሲያልቅና የታዘዘው እስኪመጣ ድረስ ብቻ ቀጠሮ እንደሚሰጡና ቅድምያ ክፍያ እንደማይጠይቁ አቶ ቢኒያም ተናግሯል፡፡
“ብዙ ጊዜ ገንዘብ ተቀብለን ቀጠሮ አንሰጥም። በዚህም ደንበኞች ይመርጡናል፡፡ ሌላው ጥሩ ነገር ደግሞ 6ሺህ የቀለም ዓይነት መያዛችን ነው፡፡ ሰዎች የተለያየ የቀለም ምርጫ ስላላቸው፣ መኪናው ቀለም ከመቀባቱ በፊት፣ ደንበኞች የፈለጉትን የቀለም ዓይነት እንዲመርጡ ዕድል እንሰጣቸዋለን። ድርጅቱ ከሚቀባቸው አምስት ቀለሞች ውጭ ደንበኛው የመረጠውን፣ ለመቀባት የአንድ ሳምንት ቀጠሮ እንሰጣለን፡፡ ይህም ተመራጭ አድርጐናል” በማለት አብራርቷል፡፡
ድርጅቱ፤ ከቀረጥ ነፃ መኪና እንዲያስገቡ ለተፈቀደላቸው ድርጅቶችም አገልግሎት ይሰጣል። “እኛ የመኪና አካላትን የምናስገባው ቀረጥ ከፍለን ነው፡፡ ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች፣ የመኪኖቹ አካላት አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ማዘዝ አለባቸው፡፡ እኛም ፈቃዱን አሳይተን ‘እነዚህን መኪኖች የምናስገባው ከቀረጥ ነፃ ነው’ ብለን ቀረጡን ማስቀረት እንችላለን” ብሏል አቶ ቢኒያም፡፡
ከበላይአብ ሞተርስ በፊት መኪና መገጣጠምና ሪልእስቴት የጀመሩ ድርጅቶች የገቡትን ቃል ሳያከብሩ ከአገር በመውጣታቸው መኪና ለመግዛትና ቤት ለማሠራት ገንዘብ የከፈሉ ሰዎች ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በዚህ ድርጅት አስቀድሞ ገንዘብ መክፈል ባይኖርም፣ አንዳንድ ሰዎች “መኪና ገዝቻቸው ካገር ቢጠፉ መለዋወጫ አላገኝም” የሚል ስጋት ሊያድርበት ይችላል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ችግር ምን ምላሽ ይኖራቸው ይሆን?
“የመለዋወጫ ችግር እንዳለ ጥናት አድርገን ስለነበር፣ መኪኖችን ከመገጣጠማችን በፊት የተለያዩ የመኪና አካላትና መለዋወጫቸውን አንድ ላይ ስላዘዝን ከእኛ መኪና የገዙ ደንበኞች አንዳችም ችግር አልገጠማቸውም፡፡ ለምንሸጣቸው መኪኖች የሁለት ዓመት ወይም የ40 ሺህ ኪ.ሜ ዋስትና እንሰጣለን፡፡ ኅብረተሰቡ በዚህ ዘርፍ በተፈጠረው ችግር የተነሳ፣ በተለያዩ ጊዜያት ስጋታቸውን ሲገልጹ ሰምተናል፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ድርጅት ያለው አቅም ምንድነው ብሎ መገምገም ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ኢንቨስትመንት ሌላ ምን አለው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አንድ ኢንቨስትመንት ብቻ ከሆነ ዘግቶ ሊሄድ ይችላልና ነው፡፡
“በላይአብ ሞተርስ ከእርሻ እስከ ማኒፋክቸሪንግና ሆቴል ኢንዱስትሪ የተሠማራ ድርጅት ነው፡፡ በላይአብ አንድ ነገር ሠርቶ አላቆመም፤ በማስፋፋት ላይ ነው ያለው፡፡ ከዚህ ፋብሪካ ጐን በ50ሺህ ካሜ ቦታ ላይ ትልቅ የኬብል ማኑፋክቸሪንግ እየሰራ ነው፡፡ ቦሌ አካባቢ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል እየተገነባ ሲሆን በዚህ ዓመት ይመረቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ፓዌ ላይ የእርሻ ልማት፣ በአዳማ ደግሞ የዶሮ እርባታ አለው፡፡ ኒኮን የተባለ የኮንስትራክሽን ድርጅትም ከፍተናል፡፡ ሌሎች ሊሠሩ የታቀዱና በጥናት ላይ የሚገኙም ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የበላይአብን አቅምና ለአገር ልማት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ መኪኖቻችንን ለሰው በዱቤ ስንሰጥ የእኛ ገንዘብ ሰው ጋ አለ እንጂ እኛ ጋ የሰው ገንዘብ የለብንም፡፡ ገንዘባችንን በትነን የት ነው የምንሄደው? ስለዚህ በላይአብ እምነት የሚጥሉበት እንጂ አገር ጥሎ በመጥፋት የሚጠረጠር ድርጅት አይደለም” በማለት አቶ ቢኒያም ድርጅቱ ያለበትን ደረጃ አብራርቷል፡፡
አቶ መስፍን ብዙነህ፣ የድህረ ሽያጭ ጥገና አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ቃሊቲ በሚገኘው የተንጣለለ የድርጅቱ ዎርክሾፕ በዋነኛነት የሚሰጠው አገልግሎት ድርጅቱ ለሸጣቸው ተሽከርካሪዎች ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ድርጅቱ ለመጣ ማንኛውም ተሽከርካሪ የጥገናና የሰርቪስ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡
የመለዋወጫ ግብይት፣ የመጫንና የማውረድ አገልግሎት እንደሚሰጡም አቶ መስፍን ገልፀዋል። ከሚገጣጥሟቸው መኪኖች በተጨማሪ፣ ፉቶን ዳምትራክ፣ ፉቶን ፒክአፕ በብቸኝነት የሚያስመጣው በላይአብ ነው፡፡ ሲኖ ዳም ትራክም፣ ያስመጣሉ፡፡ ከከባድ መሳሪያ ደግሞ ሎደርና ግሬደር በኮንቴይነር አስመጥተው በወርክሾፑ ይገጣጥማሉ፣ የሰርቪስና የጥገና አገልግሎት እንደሚሠጡም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
የበላይአብ የወደፊት ዕቅድ የሚገጣጥማቸውን መኪኖች ለምሥራቅ አፍሪካ ገበያ በማቅረብ ለአገሩ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ነው፡፡ “ይህን ለማድረግ ኅብረተሰቡና ደንበኞቻችን በሚገባ ሊያውቁን ይገባል፡፡ በአንድ ወይም በጥቂት ድርጅቶች የተፈጠረ ጥፋት፣ በሁሉም ድርጅቶች ይፈጠራል ብሎ ማሰብ አይገባም፡፡ ሌላው ደግሞ ሰዎች አመለካከታቸውን መለወጥ አለባቸው፡፡
“የሚያወዳድሩትን ነገር ወይም ድርጅት በትክክለኛ መመዘኛ ማወዳደር አለባቸው፡፡ አንድም ኪ.ሜ ያልተነዳ፣ ጌጁ (ኪ.ሜ ቆጣሪው) ዜሮ ላይ ያለ አዲስ መኪናና ከ25 ዓመት በፊት ተመርቶ በየበረሃው ጨው የበላውን መኪና ከመግዛት በፊት ቆም ብሎ በማሰብ እውነታውን መረዳት ያስፈልጋል። እውነቱን ሳይለዩ በአሉባልታ መመራት በጣም መጥፎ ባህርይ ነው፡፡
ነገሮችን የማጥላላት ባህርይ ያለው ሰው “መጥፎ ነው” ያለውን ከመቀበል፣ የእኛን መኪኖች የገዙ ሰዎችን በማነጋገር ስለመኪኖቹ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ይበጃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ገበያው ሁሉ በአሉባልታ የተሞላ ይሆናል፡፡ ችግሮች እንኳ ቢኖሩ ከአገር አኳያ ማየትና ችግሩን በመነጋገር መፍታት ነው የሚሻለው። ድርጅቱ ዛሬ ባያተርፍ ለመጪው ትውልድ መነሻ ትተን ነው የምናልፈው፡፡ ከዚህ አንፃር ነው መታየት ያለበት” በማለት የመገጣጠሚያው ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የበላይአብ ሞተርስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ግርማ ደግሞ በቀጣዩ ዓመት የሥራ አድማሳቸውን በማስፋት የሚገጣጥሟቸውን ተሽከርካሪዎች ወደጐረቤት አገሮች ለመላክ፣ በሀገር ውስጥም፣ አካባቢን የማይበክሉ አዳዲስ ሞዴል ተሽከርካሪዎችን ለማቅረብ ማቀዳቸውን ገልፀዋል፡፡

Saturday, 19 October 2013 12:08

ሕይወት በማህፀን ዓለም

            አንድ ልጅ ተፀንሶ እስኪወለድ ድረስ ያለው የሰው ልጅ ዕድገት ፍጥነት በጣም አስገራሚና የሚደንቅ ነው፡፡ በአንደኛው ወር ብቻ በጣም ኢምንቷ ኦርጋኒዝም (አንዱ ከሌላኛው አካል ጋር የሚደጋገፉ ጥቃቅን ኅዋሳት) በተፀነሰበት ወቅት ከነበረው ክብደት 10ሺህ ያህል ጊዜ ይጨምራል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት፣ ከኢምንት ውሃማ ነገር፣ ቁጥር ስፍር ወደሌለው ውስብስብና ጅምር የሰው ቅርፅ ይለወጣል፡፡ ቅርፁ ባይጠናቀቅም ልጅ እንደሚሆን ግን መገንዘብ ይቻላል፡፡
እያንዳንዱ ሂደት ይሆናል ብሎ ለማመን የሚከብድና ግምትን የሚፈታተን ረቂቅ የዕድገት ለውጥ ነው፡፡ አንደኛው የለውጥ ሂደት ለሚቀጥለውና ለዋነኛው ሁለንተናዊ ዕቅድ፣ በሚያስገርም ፍፁም ትክክለኛነት ያስተላለፋል። ይህ 267 ያህል የሚፈጀው የትራንስፎርሜሽን ወይም የለውጥ ሂደት፣ የራስና የማንኛውም ሰው የማይታመን የሕይወት ታሪክ የሚጀመርበት የዕድገት ሂደት ነው፡፡
ተቃራኒ ፆታ የሆኑ ሰዎች ወሲባዊ ግንኙነት በሚፈፅሙበት ጊዜ፣ ያኮረተ ወይም ለመፀነስ ዝግጁ የሆነ የሴቷ እንቁላል፣ ከወንዱ የዘር ፍሬ (ስፐርም) ጋር ሲገናኝ ወዲያውኑ ከመቀፅበት፣ የሴቷን ባህርያት የያዙ 23፣ የወንዱን ባህርይት የተሸከሙ 23፣ እንዲሁም ሁለት ፆታ ወሳኝ ከሆኑ ክሮሞዞሞች (የዝርያ ሐረግ) ጋር በመሆን 48 ክሮሞዞሞች፣ የተሟላ የዘር ሐረግ ባቀፈው ሴል (ኅዋስ) እምብርት ሆነው የመጀመሪያውን የኅዋስ ክፍፍል (ሴል ዲቪዥን) ለመጀመር በከፍተኛ ፍጥነት በመሽከርከር ይዋሃዳሉ፡፡
የእናቱንና የአባቱን የዘር ውርስ ይዞ የተፀነሰው እንቁላል መጠን በጣም የሚገርም ነው፡፡ በእንግሊዝኛው ፊደል አይ (i) አናት ያለችውን ነጥብ የሚያክል ነው፡፡ ነገር ግን ይቺ ኢምንት ፅንስ፣ ከሁሉም ልጆች ልዩ የሆነውን ልጅና ከማንኛውም ወላጅ ልዩ የሆኑትን የእናቱንና የአባቱን የወ/ሮና የአቶ እገሌን የዘር ሐረግ አጠቃላ ይዛለች፡፡
ኅዋሳቱ መከፋፈል ሲጀምሩ (አንዱ ሴል ሁለት፤ ሁለቱ አራት፤ አራቱ ስምንት፣ … እያለ ይቀጥላሉ) ፅንሱ በሴቷ ግራና ቀኝ ጐን በሚገኙት የእንቁላል መተላለፊያና የፅንስ መፈጠሪያ (ፋሎፒያን ቲዩብ) በአንዱ ውስጥ እየተንሳፈፈ ወደ ማኅፀን ጉዞ ይጀምራል፡፡ ከቲዩቡ እስከ ማኅፀን ያለው ርቀት 5 ሳ.ሜ ያህል (2 ኢንች) ቢሆንም፣ ፅንሱ ማኅፀን ለመድረስ ሦስት ወይም አራት ቀናት ይፈጅበታል፡፡ ብዙ ጊዜ ፅንሱ ማኅፀን የሚደርሰው በ16ኛው የኅዋስ ክፍፍል ደረጃ ነው፡፡
በእነዚህ የመጀመሪያ ቀናት እንኳ አስገራሚ ለውጥና ዕድገት ስለሚካሄድ ሁለት የተለያዩ ሴሎች በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹትንና የልጁን የውጪኛ አካላት የሚፈጥሩትን፣ ዝርግና በፍጥነት ጠላቂ ኅዋሳትና የልጁን የውስጠኛ አካላት የሚፈጥሩ ክብና የሚያምሩት በዝግታ ጠላቂ ኅዋሶች ይፈጠራሉ፡፡
ከአራተኛው እስከ ስድስተኛው ወይም ሰባተኛ ቀን ድረስ የፅንሱ መጠን ከነጥብ ከፍ ብሎ የስፒል (የወረቀት መርፌ) አናት ያህላል፡፡ በዚህ ጊዜ የኳስ (ኤግ ቦል) ቅርፅ የያዘው እንቁላል፣ በሙቅና በጥቁር ፈሳሽ በተሞላው ማኅፀን ውስጥ ይንሳፈፋል፡፡ ልስልሱ የማኅፀን ግድግዳ ከጥቃቅን የደም ስሮች ጋር ተጠላልፎ ይሰራል፡፡ ፅንሱ በዚህ ልስልስ ግድግዳና ስፖንጅ በመሰለ ነገር ላይ ይጣበቅና ራሱን በኃይል ይቀብራል፡፡ ከዚያም፣ በማቆጥቆጥ ላይ ካሉት ጥቃቅን ፀጉር መሰል ነገሮች (ካፒላሪስ) ጥቂቶቹን በመክፈት በውስጣቸው የያዙትን ደም ያስወጣል፡፡
ኳስ መሰሉ እንቁላል (ፅንስ) በመቶዎች የሚቆጠሩ በጣም ጥቃቅንና በፍጥነት አዳጊ ቪሊ (Villi) የተባሉ ፀጉር መሰል ነገሮች በመላ አካሉ ላይ ያበቅላል፡፡ ጥቃቅን ተክሎች ስራቸውን በጥልቀት ሰደው ምግብ እንደሚስቡት፣ ቪሊዎቹም፣ ስራቸውን እጅግ ጥቂት በሆነው ደም ውስጥ ተክለው ኦክስጂንና ምግብ ይመጣሉ፡፡ ምግቡም፣ ኳስ መሰሉን እንቁላል በፍጥነት ያሳድገዋል፡፡
እነዚህ ሁሉ ለውጦች ሲከናወኑ እናቲቱ ማርገዟን እንኳ አታውቅም፡፡ ምክንያቱም ቢያንስ ከ21ኛው ቀን በፊት ማርገዟን ማወቅ ስለማትችል ነው፡፡
በዚህ ጊዜ፣ ሞለል ያለው ማኅፀን ውስጥ የሚገኙት በርካታ ክብ ሴሎች፣ ራሳቸውን ወደ ትናንሽ አስኳልና አሚኒዮ (aminion) ከረጢትነት ይለውጣሉ፡፡ ከረጢቶቹ በሚነካኩበት (በሚገናኙበት) ስፍራ ደግሞ ሦስተኛ ከረጢት ይፈጥሩና ባለ ሦስት ደረጃ ሞላላ ንጣፍ ይፈጥራሉ። አሚንዮ ከረጢቱ ልጁ እስኪወለድ ድረስ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ ቢሆንም የአስኳል ከረጢቱ ግን ወደፊት ምንም ጥቅም የለውም፡፡ አሁን ራሱን ወደ ሽል እስኪለውጥ ድረስ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወተው ቀለል ያለው ባለ ሦስት ደረጃ ኅዋስ (ሴል) ነው፡፡
እያንዳንዱ ንብርብር ንጣፍ ወደፊት ልጅ ለሚሆነው ሽል የተለያየ ኅዋስ መፍጠሪያ ይሆናል። አንደኛው ንጣፍ የነርቭ ሲስተም፣ ቆዳ፣ ፀጉር፣ የጣት ጥፍር፣ የጥርስ መስተዋት፣ የአፍንጫና የጉሮሮ ግድግዳ ሴሎች መፍጠሪያ ይሆናል፡፡ መካከለኛው ንጣፍ፤ የሽሉ ጡንቻ፣ አጥንትና ጅማት፣ ደምና የደም ስሮች፣ ኩላሊትና የድድ መፍጠሪያ ሴል ይሆናል። ሦስተኛው ንጣፍ ደግሞ አንጀትና ለአብዛኛው መተንፈሻ አካላት ሲስተም መስሪያነት ይውላል፡፡
ቀጣዩ ለውጥ ወይም ትራንስፎርሜሽን ደግሞ፣ ምናልባት ከሁለም የላቀው ተአምራዊ ሂደት ነው፡፡ በ19ኛው ወይም በ20ኛው ቀን፣ ሞለል ያለው ክብር ነገር፣ በአካሉ ላይ በሁለቱም በኩል ወደታች የሚሄድ ጐድጐድ ያለ ቦይ መሳይ ነገር ይፈጠራል፡፡ ቦዮቹ በአንድ ጫፍ ይገናኛሉ፤ ያ የልጁ ራስ መሆኑ ነው። ቦዮቹ ከፍና ዝቅ እያሉ በመተጣጠፍ ሲቀራረቡ ሞላላው ክብ ነገር የግማሽ ጨረቃ ወይም የደጋን ቅርፅ ይይዛል፡፡ የደጋኑ የውጪኛ እጥፋት (Curve) የልጁ ጀርባ ይሆናል፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ደግሞ አከርካሪን የሚጠቁም ነገርና አዕምሮ ውስጥ የሚገኙ ነገሮች፣ በራስ መጨረሻ የሚገኘውን ጐድጐድ ያለ ስፍራ ሙላት ይጀምራሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅና እግር መሆኑን የሚጠቁሙ ትናንሽ ቡጥ መሰል ነገሮች ማቆጥቆጥ ይጀምራሉ፡፡ በ21ኛው ቀን፣ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ የሆነው ልብ ይፈጠራል፡፡ ከዚያም ያ ልብ ከ10 ቀናት በኋላ መምታት ይጀምራል፡፡
ፅንሱን የያዘው ሞለል ያለ ከረጢት (እንግዴ ልጅ) ከእናቲቱ ጋር የሚገናኘው፣ በእትብት ነው፡፡ እትብቱ የተሠራው ደግሞ እንደክር ወይም ገመድ በተጠላለፉ ኅብረ-ሴል (Tissues) ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእትብቱ ርዝመት እስከ 56 ሳ.ሜ (22 ኢንች) ሊደርስ ይችላል፡፡ በፕሮቲን ፈሳሽ (aminotic sac) በተሞላው ሞለል ያለ ከረጢት (እንግዴ ልጅ) ውስጥ የግማሽ ጨረቃ ወይም የደጋን ቅርፅ ያለው በጣም ትንሽ ሽል በኅብረ-ሴል ከረጢት ሁለቴ ተጠቅልሎና በሌላ የኅብረ-ሴል ኳስ ውስጥ ሆኖ፣ እንደስፖንጅ በሚለሰልሰውና በሚመቸው የማኅፀን ግድግዳ ራሱን ይቀብራል፡፡ 98 በመቶ ንፁህ ውሃ በሆነ ፈሳሽ የተሞላው ከረጢት (እንግዴ ልጅ) ተግባር፣ የሽሉ መቀመጫ ቤት ብቻ ሳይሆን፣ ንቅናቄንም (Shock) በማርገብ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሽሉ በፍጥነት የልጅ ገጽታ እየያዘ ይሄዳል፡፡ በሁለተኛው ወር፣ ከራስ እስከ መቀመጫው (ቂጥ) ያለው ርዝመት 2ሳ.ሜ ተኩል (1 ኢንች) ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን አፍንጫ፣ አፍ፣ ጆሮና ዓይን ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ጐድጐድ ያለ ነገር አለው፡፡ ከሦስተኛው ወር መጨረሻ ጀምሮ ሽሉ፣ ከ7ሳ.ሜ ተኩል በላይ (3 ኢንች) ሲረዝም፣ ክብደቱ ደግሞ ከ28 ግራም በላይ ይሆናል፡፡ የተለያዩ የአካል ሲስተሞቹም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ በግልፅ ያሳያሉ ወይም ይለያሉ። በዚህ ጊዜ ዓይንና ሽፋሽፍቱ የተፈጠሩ ቢሆንም ዓይኑ ግን ለጊዜው እንደተከደነ ነው፡፡ ፆታም ይለያል፡፡ የእጅና የእግር መፈጠር ከመጠናቀቁም በላይ ሁለቱም ጣቶች ጥፍር አብቅለዋል፡፡ ሽሉ እጅ እግሩን ማንቀሳቀስ ቢጀምርም፣ እናቲቱ ግን ይህን የመጀመሪያ ጊዜ እንቅስቃሴ መገንዘብ አትችልም። ለሁለት ወራት ሲመታ የቆየው ልብ ጡንቻም ጠንክሯል፡፡
በዚህ ጊዜ ሽሉ መዋጥ ብቻ ሳይሆን መተንፈስን ለመለማመድ ይመስላል፣ ዙሪያውን ከከበበው የፕሮቲን ፈሳሽ ጥቂት ይጐነጫል፡፡ ፈሳሹ ወደ ሳንባው ሲገባ፣ ሽሉ የመተንፈሻ ጡንቻዎቹን በመጠቀም ያስወጣዋል፡፡ ይህ ሁሉ ልምምድ ሲሆን፣ ሽሉ እስኪወለድ ድረስ ኦክሲጅንና ምግቡን የሚያገኘው ከእናቱ ነው - በእትብት አማካኝነት። እነዚህ ሁሉ አስገራሚ ለውጦችና ዕድገቶች የሚከናወኑት በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ነው፡፡ አሁን የእናቲቱ ማኅፀን ማደግ ቢጀምርም ምናልባት በራሷ ዓይነ ካልሆነ በስተቀር የሆዷን ማደግ ሌሎች አይገነዘቡትም፡፡ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ሽሉ ወደ ልጅ መጠን የሚያድግ ሲሆን አዲስ ልጅ ሆኖ ሲወለድ የሚያደርገው ነገር ችሎታም ቀስ በቀስ ያድጋል፡፡
እናትና ሽሉ የሚገናኙት በእትብት ብቻ ነው። እትብቱ ነርቭ ስለሌለው፣ የእናትና የሽል ነርቭ ሲስተሞች በጭራሽ አይገናኙም፡፡ ስለዚህ፣ እናቲቱ የምታስበው ወይም የምታየው ነገር ሽሉን በፍፁም አያውከውም፡፡ ስለዚህ፣ ሰው አካል ላይ ጠቆር ወይም ነጣ ያለ ነገር ሲኖር፣ “እናቱ እሷን ወይም እሱን እርጉዝ ሆና የሆነ ነገር ሲያምራት የዳበሰችው ወይም የነካችው ቦታ “ሽታ” ነው” የሚለው ብዙ ዘመናት ያስቆጠረው አፈ-ታሪክ ውሸት ነው ማለት ነው። የሽሉ የነርቭ ሲስተም፣ በእናትየው ጋር በፍፁም እንደማይገናኘው ሁሉ፣ የደም ዝውውር ሲስተሙም ከእናቱ ጋር ፈፅሞ የተለያየ ነው። ሽሉ፣ ከእናቱ ጋር በጭራሽ የማይገናኝና የራሱ የሆነ ደም ነው የሚያመርተው፡፡ ሁለቱ የደም ዝውውሮች (እናትና ሽሉ) ኦክስጅንም ሆነ ምግብ የሚለዋወጡት፣ በእርግዝና ወቅት በማኅፀን ውስጥ በሚፈጠርና እንደተወለደ በሚበጠሰው እትብት ነው፡፡ በሽሉ እንብርት ላይ ተጣብቆ የሚገኘው እትብት ከ12 እስከ 15 ሳ.ሜ ርዝመት ሲኖረው፣ ቪሊ በተባሉ ጥቃቅን የደም ስሮች የተሠራ ነው፡፡ የሽሉ መተንፈሻና ምግብ መፍጫ ሲስተሞች ዕድገት ዘገምተኛ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ወደፊት የሚወለደውን ልጅ ወክሎ የሚተነፍሰውና ምግብ የሚፈጨው እትብት ስለሆነ ለ ሽሉ የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛና በዋጋ ሊተመን የማይችል ነው፡፡
እናቲቱ የሽሉ እንቅስቅሴ የሚሰማት በአራተኛው ወር መጨረሻ ገደማ ነው፡፡ መጀመሪያ አካባቢ እንቅስቅሴው በጣም ደካማ በመሆኑ የሽሉ እጅና እግር እንቅስቃሴ ጠንከር ለማለት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል፡፡ አሁን በእርግዝናው አጋማሽ ነን እንበል፡፡ በዚህ ጊዜ ሽሉ 15 ሳ.ሜ ርዝመትና 170 ግራም ክብደት ይኖረዋል፡፡ ቅንድብና ሽፋሽፍቱ መታየት ይጀምራሉ፡፡ የልብ ምቱ ጠንከር በማለቱ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በልብ ምት ማዳመጫ (ስቴትስኮፕ) ሊሰማ ይችላል፡፡ ልቡ በአንድ ደቂቃ 136 ጊዜ ይመታል፡፡ ይህም የእናቱን ልብ ምት እጥፍ ያህል ማለት ነው፡፡
ሽሉ ፣ በ6ኛው ወር መጨረሻ አንድ ማስመርያ ያህል ርዝመትና ግማሽ ኪ.ግ ያህል ክብደት ይኖረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ፣ ሲታፈን ድምፅ ማሰማት፣ የፊት ጡንቻዎቹን ማንቀሳቀስና ማስነጠስ ይችላል። ዓይኖቹ የተሟላ ዕድገት ላይ ቢደርሱም፣ ብርሃን ብቻ ነው የሚለዩት፡፡ አሁን ሽሉ በሚያስደንቅ ሁኔታ ጥንካሬ በማምጣት፣ አካሉን መዘረጋጋትና እራሱን ማገላበጥ ይችላል፡፡ የደረት ጡንቻዎቹ በየዕለቱ ለመተንፈስ በሚያደርጉት ዝግጅት ይበልጥ እየጠነከሩ ነው፡፡ ኩላሊቶቹ ለማጣራት፣ አንጀቱ ምግብ ለመፍጨት ዝግጁ ቢሆኑም፣ ቆሻሻ ማስወገጃ ስለሌለ መደበኛ ሥራቸውን የሚጀምሩት ልጁ ሲወለድ ነው፡፡ ሽሉ ከተወለደ በኋላ የተፈጥሮ ግዴታ የሆነውን አበላል ለመለማመድ (ያለ ማቋረጥ ማለት ይቻላል) የመጥባት እንቅስቅሴ ያደርጋል፡፡ አንዳንድ ልጆች ከመወለዳቸው በፊት እንደሚያደርጉት አውራ ጣቱን ሊጠባ ይችላል፡፡
በዘጠነኛው ወር መጨረሻ አካባቢ ወይም በ252ኛው ቀን ገደማ ሽሉ የሆድ ውስጥ ዕድገቱን ጨርሶ ለመወለድ ዝግጁ ይሆናል፡፡ ፅንስ ተፈጥሮ ለመወለድ 267 ቀናት ይፈጃል የሚባለው አማካይ ስሌት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ልጁ “ይወለዳል” ተብሎ ከሚጠበቅበት ቀን፣ 15 ቀናት ቀድሞ ወይም ዘግይቶ ሊወለድ ይችላል፡፡
ሊወለድ የደረሰ ሽሉ ብዙውን ጊዜ ከ2 ተኩል እስከ 3 ኪ.ግ ሲመዝን፣ 48 ሳ.ሜ ወይም አንድ ማስመሪያ ያህል ቁመት ይኖረዋል፡፡ በማኅፀን ውስጥ ያለው ቦታ እንዲበቃው፣ የእጁን ክንዶች ደረቱ ላይ አጥፎ ሲያስቀምጥ፣ ጭኖቹን ደግሞ ኩርምት ብሎ ሆዱ ላይ ያኖራል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እንቅልፍ ላይ የሆነ ይመስል ፀጥተኛ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን፣ እጅና እግሮቹን ሲያንቀሳቅስ እናቲቱ የሚሰማት ግፊት ኃይለኛ ነው፡፡ እርግዝናውን የሚከታተለው ሐኪም ሽሉ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ፣ የእጁን መዳፍ እናቲቱ ማህፀን ላይ ቢያሳርፍ ሽሉ ዝም የሚል እንዳይመስላችሁ፤ እጁን በማወራጨት የቦክስ ምላሽ በመስጠት ተቃውሞውን ይገልፃል፡፡
በዚህ ጊዜ ሽሉ ትንሽ፣ ነገር ግን የተሟላ የሰው ልጅ ፍጡር ነው፡፡ አሁን፣ በማንኛውም ቀን ለመወለድ ወይም ወደዚች ዓለም ለመምጣት፣ ማንነቱን የሚፈታተን የመጀመሪያውን ፈታኝ ሁኔታ ይጋፈጣል፡፡ አሁን የሚጠበቀው የእሱ መምጣት ወይም መወለድ ነው፡፡ እናቱ ማኅፀን ውስጥ ሆኖ ያካበተውን የሚደንቁ ተግባራዊ ልምዶች ከተወለደም በኋላ ይቀጥላል፡፡ በአጭሩ፣ የማንኛውም ሰው ሕይወት፣ ከመወለዱ በፊት ይህን ነው የሚመስለው፡፡

Published in ዋናው ጤና

ህፃናት በተቅማጥ በሽታ ሲጠቁ በአፋጣኝ የሰውነታቸውን ፈሳሽ በመተካት ከሞት የሚታደጋቸውና አቅማቸው እንዲመለስ የሚያደርገው የኦ.አር.ኤስ እና ዚንክ ውህድ የሆነ “ለምለም ፕላስ” የተሰኘ አዲስ ምርት ገበያ ላይ ዋለ፡፡
በዲኬቲ ኢትዮጵያ ተዘጋጅቶ ለገበያ የቀረበው አዲስ ምርት፤ ህፃናት በተቅማጥ በሽታ በሚጠቁበት ጊዜ ከሰውነታቸው የሚወጣውን ፈሳሽ ከመተካትና አቅማቸውን ከመመለስ ባሻገር በተከታዮቹ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ በተቅማጥ በሽታ የመያዝ ዕድላቸውን የሚያስወግድና የሚከላከል መሆኑ ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም ውህዱ ህፃናቱ በተቅማጥ በሽታ ቶሎ ቶሎ እንዳይያዙ የሚያደርግ አቅም እንደሚገነባላቸውም ተገልጿል፡፡
ምርቱ የተዘጋጀው ዲኬቲ ኢትዮጵያ በማይክሮ ኒውትሬት ኢንሺየቲቭ በኩል በአለማቀፍ የካናዳ መንግስት የልማት ትብብር በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን በአገር ውስጥ እየተመረተ አገልግሎት ላይ እንደሚውልም ተገልጿል፡፡ ስርጭቱ የሚከናወነው በዲኬቲ ኢትዮጵያ ሲሆን በመንግስትና የግል ተቋማትና የመድሃኒት መሸጫ መደብሮች ውስጥ በማከፋፈል ለህብረተሰቡ እንዲዳረስ እንደሚደረግ ከትላንት በስቲያ በሂልተን ሆቴል በተካሄደ የምርት ማስተዋወቂያ ስነስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

Published in ዋናው ጤና

            ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዚሁ ጋዜጣ “ፔን” በተባለ ከደራሲያን ጋር በሚሰራ ድርጅት ጋባዥነት አይስላንድ የተባለችውን አውሮፓዊት ሀገር ጐብኝቶ የመጣ አንድ ወዳጃችን በዋና ከተማዋ ሬይካቪክ በቆየባቸው ቀናት ከተመለከታቸው ነገሮች ውስጥ ይበልጥ ትኩረቱን የሳቡትን ለይቶ በመፃፍ አስነብቦን ነበር፡፡ 

በአይሁዶች ሚሽናህ “ካለው ላይ የጨመረ እርሱ የአባቱን ምርቃት፣ የእናቱንም እቅፋት ያገኛል” የሚል የቅድስና ቃል ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህ የዛሬው የእኔ ጽሑፍም አይስላንድ ስለተባለችውና በለምአቀፉ ሚዲያ በክፉም ሆነ በበጐ አዘውትሮ ስሟ ሲነሳ ስለማንሠማት አውሮፓዊት ሀገር በርካታ ነገረ ስራዎች ውስጥ የእኔን ትኩረት ይበልጥ የሳቡትን ጉዳዮች በማንሳት ከሳምንታት በፊት ወዳጃችን ከሰጠን ላይ ለመጨመር ነው፡፡ አይስላንድ ከአለማችን ሰሜናዊ ጫፍ በቅርብ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ቅርበቷ በቅዝቃዜና በበረዶ የተሞላች ሀገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡
ይህ በረዶና ቅዝቃዜዋ እነሆ የስሟ መጠሪያ ለመሆንም በቅቷል፡፡ እንዲህ ያለው የአይስላንድ መልክአምድራዊ አፈጣጠሯ አብዛኛውን ጊዜ በደንብ ለማያውቋት ወይም ላይ ላዩን ብቻ የሚያውቋት ሰዎች ልክ ወዳጃችን ባለፈው ጊዜ ጽፎ እንዳስነበበን ዋነኛ ትኩረታቸውን በአየር ንብረቷና ከአየር ንብረቷ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ዋነኛ ምክንያት ሆኖአቸዋል፡፡
ይህ ግን አሳሳች ነገር ነው፡፡ በርካቶች አይስላንድን በአንድ ጐን ወይም በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያዩዋት አድርጓቸዋል፡፡ የምዕራብ አፍሪካ ነዋሪዎች “ከሁሉም ምርጥ የሆነው ዛፍ ጭው ካለው ገደል አፋፍ ላይ ይበቅላል፡፡” የሚል አባባል አላቸው፡፡ ይህ አባባል አይስላንድን ምናልባት ከሌላው በተሻለ ሊገልፃት ይችላል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ አይስላንድ ጥልቅ ከሆነው ገደል አፋፍ ላይ የበቀለች ምርጥ ዛፍ ናት፡፡ በበርካታ ዘርፍ ያሉት ነገረ ስራዎቿ ይህንን እውነታ በሚገባ ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡
አንድ መቶ ሶስት ሺ ስኩዌር ኪሎሜትር በሚሆነው ጠቅላላ መሬቷ ላይ ሶስት መቶ ሃያ አንድ ሺ ስምንት መቶ ሃምሳ ሰባት የሆነው ጠቅላላ ህዝቧ ሰፋ ሰፋ ብሎ በመስፈር ይኖራል፡፡ ይህም ዘርዛራ የህዝብ አሰፋፈር ካላቸው የአውሮፓ ሀገራት መካከል ቀዳሚ እንድትሆን አስችሏታል፡፡
የአይስላንድ ባህል ከሀገሪቱ የኖርስ ቅርስ የተወረሰ ነው፡፡ አብዛኛዎቹን አይስላንዳውያን ስለዘር ሀረጋቸው ብትጠይቋቸው ከኖስና ጋይሊክ (ሴልቲክና ሻይኪንግ) ሰፋሪዎች የመጡ ወይም የሚመዘዝ መሆኑን አስረግጠው ይነግሯችኋል፡፡
የማንነታቸውን ስረ መሠረት ጥንቅቅ አድርገው የሚያውቁት አይስላንዳውያን ደግሞ የመጀመያው የኖርስ ሰፋሪ ኢንጐልፈር አርናርሰን እንደሚሰኝና የሰፈራ ዛኒጋባውንም በስምንት መቶ ሰባ አራት አመተ ምህረት ዛሬ የአይስላንድ ዋና ከተማ በሆነችው በሬይካቪክ ቀልሶ መኖር እንጀመረ በሚገባ ያብራሩላችኋል፡፡ ይህንን ታሪክ የሚነግሯችሁ ደግሞ እንዲሁ በወሬ ብቻ ሳይሆን በቁፋሮ የተገኙ ታሪካዊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ነው፡፡
የአየር ንብረት ተመራማሪዎች በቀደሙት የኖርስና ጋይሊክ (የሴልቲክና ቫይኪንግ) ሰፋሪዎች ጊዜ የአይስላንድ የአየር ንብረት አሁን ካለው እጅግ በተሻለ ሞቃት እንደነበረ፤ አሁን ያለው አንድ በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የደን ሽፋን ያኔ ሃያ አምስት በመቶ እንደነበረ በማስረጃ አስደግፈው ይናገራሉ፡፡
አይስላንዳውያን በዘጠኝ መቶ ሰላሳ አመተ ምሕረት የአይስላንዲክ ኮመንዌልዝን እንዲቆጣጠር ያቋቋሙት የህግ አውጭና፣ የህግ አስፈፃሚ ምክር ቤት ወይም ፓርላማ ህልውናውን እንደጠበቀ እስከ አስራ ሶስተኛው ክፍለዘመን ድረስ መዝለቅ ችሎ ነበር፡፡
በስተርላንግ ዘመን የተፈጠረው የውስጥ ትግልና የእርስ በርስ ግጭት በ1262 ዓ.ም ዛሬ “የድሮው ስምምነት” እየተባለ ለሚጠራው ውል መፈረም ዋነኛ ምክንያት ሆነ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ውል ተራ ውል አልነበረም፡፡ ራሷን ችላ ትኖር የነበረችው አይስላንድ በኖርዌይ የዘውድ መንግስት ስር እየገበረች እንድታድር የሆነችው በዚህ ስምምነት አማካኝነት ነበር፡፡
ከዚህ ክስተት በሁዋላ የተከተሉት አመታት ለአይስላንድና ለህዝቦቿ መልካም አመታት አልነበሩም፡፡ የአየር ንብረቷ ቀስ በቀስ ግን ባልተቋረጠ ፍጥነት እየቀዘቀዘና እየከፋ ሄደ፡፡ በተከታታይ የደረሱበት የእሳተ-ገሞራ ፍንዳታዎች፣ከግግሩ በረዶ ጋር ተዳምሮ ቀላል የማይባል መጠን ያለውን መሬት ለእርሻ አገልግሎት እንዳይውል አደረገው፡፡ ሰፊ ይባል የነበረው የደን ሀብትም በከፍተኛ ፍጥነት እየተመናመነ ሄደ፡፡
ይህ ሁኔታ የአይስላንዳውያንን የእለት ተዕለት ህይወት እጅግ መራራና ሸክሙ የማይቻል ከባድ እዳ አደረገባቸው፡፡ በዚህ የተነሳም አይስላንዳውያንም ሆኑ ሀገራቸው ከአውሮፓ እጅግ ደሀ ከሆኑት ሀገራት ተርታ መሰለፍ ግድ ሆነባቸው፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በ1402 አ.ም እና በ1494 አ.ም የተከሰተውና “ጥቁሩ ሞት” እየተባለ የሚጠራው ወረርሽኝ እንዳይሞቱ እንዳይሸሩ አድርጎ ክፉኛ ደቆሳቸው፡፡ በተለይ በ1402 አ.ም የተከሰተውና ለሶስት አመት ያህል የዘለቀው የመጀመሪያው ወረርሽኝ ከጠቅላላው ህዝባቸው ከሀምሳ እስከ ስልሳ በመቶ የሚሆነውን በመፍጀት አይስላንዳውያንን ከምድረ ገፅ ነቅሎ ሊያጠፋው ክፉኛ ተገዳድሮአቸው ነበር፡፡
የናፖሊወንን ጦርነት ተከትሎ በ1814 አ.ም የተፈረመው የ“ኪየል ውል” የዴንማርክ - ኖርዌይ ግዛት ለሁለት እንዲከፈልና ራሳቸውን የቻሉ የንጉሱ ነገስት መንግስት እንዲሆኑ አደረጋቸው፡፡ በኖርዌይ አገዛዝ ስር የነበረችው አይስላንድም ዴንማርክን በአዲስ ገዢነት ተቀብላ ማደር ጀመረች፡፡
ከኖርዌይ ጋር ሲወዳደር ዴንማርክ አይስላንድን የገዛቻት ከብረት በጠነከረ ክንድ ነበር። ለአይስላንዳዊያን ግን ይህ በወቅቱ የቅድሚያ ትኩረት የሚሰጡት ጉዳያቸው አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ከዴንማርክ የጭቆና አገዛዝ ይልቅ ከግራና ከቀኝ ጎናቸውን ሰቅዞ ይዞ አላፈናፍን ያላቸውና ህልውናቸውን በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተናቸው ያለ ትልቅ ጉዳይ ከፊትለፊታቸው ተደቅኖባቸው ነበርና ነው፡፡ ይህ ትልቅ አደጋ ሌላ ነገር ሳይሆን በየእለቱ ቅዝቃዜውና የበረዶው ግግር እየከፋ የመጣው የሀገራቸው የአየር ንብረት ጉዳይ ነበር፡፡እየከፋ የሄደው የአየር ንብረት በተለይ በአስራዘጠነኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ አካባበቢ በርካታ አይስላንዳዊያን ወደ አዲሱ አለም በዋናነት ደግሞ ወደ ካናዳ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል፡፡ ለምሳሌ በ1820 አ.ም ሰባ ሺ ከሚሆኑት አይስላንዳዊያን መካከል አስራ አምስት ሺ የሚሆኑት ወደ ማኒቶባ ካናዳ ተሰደዋል፡፡ ይህ ቁጥር በሌላ አነጋገር ሲገለጽ በወቅቱ ከነበረው የአይስላንድ ጠቅላላ የህዝብ ቁጥር ከሃያ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በአንድ አመት ውስጥ ብቻ ሀገሩን ጥሎ ተሰዷል ማለት ነው፡፡
በ1943 አ.ም የሚያዚያ ወር መጨረሻ ላይ ለሀያ አምስት አመታት የዘለቀው የዴንማርክና አይስላንድ ህብረት ስምምነት ፈረሰ፡፡ በቀጣዩ አመት ግንቦት ሀያ ቀን ደግሞ አይስላንዳዊያን ከዴንማርክ አገዛዝ በመላቀቅ የራሳቸውን ነፃ ግዛት ለመመስረት ድምፃቸውን ሰጡ፡፡ ሰኔ አስራ ሰባት ቀን 1944አ.ም ላይ ደግሞ ነፃ የአይስላንድ ሪፐብሊክን በሟቋቋም ስቪን ቢዬንሰንን የመጀመሪያው ፕሬዚዳንታቸው አድርገው መረጡ፡፡
ይህ የአይስላንድ የቀድሞው ታሪኳ ነው፡፡ ከነፃነት በሁዋላ ያለው የአይስላንድ የኢኮኖሚ፣የፖለቲካ፣ማህበራዊና የአለም አቀፍ ግንኙነት ታሪኳበጣም አስገራሚ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ይህቺ ድምጿም ሆነ ወሬዋ እምብዛም የማይሰማው አውሮፓዊት ሀገር በስነ ፅሁፍ ረገድ ያላት ታሪክና ለአለም ስለፅሁፍ እድገት ያበረከተችው አስተዋፅኦ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ እነዚህን የሳምንት ሰው ይበለንና ሳምንት እንመለስበታለን፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲና ሄይንሪች ሄይን በተባለ ጀርመናዊ ዩኒቨርስቲ ትብብር በአሰላ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ የተሰራው የቆላ በሽታዎች ምርምር ማዕከል ባለፈው ረቡዕ ተመረቀ፡፡
Institute of Research for Tropical Infectious Disease የተባለው የምርምር ማዕከል፤ በጀርመን ዩኒቨርስቲ የገንዘብ ድጋፍ ተሰርቶና ሙሉ የመገልገያ ቁሳቁሶቹ ተሟልተውለት ለምረቃ በቅቷል፡፡
በአሰላ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ በተከናወነው የማዕከሉ የምረቃ ስነስርዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የአሰላ ጤና ሳይንሶች ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ዶ/ር ለገሰ ታደሰ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ በጀርመናዊው ዩኒቨርስቲ የማቴሪያል፣ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ድጋፍ የሚንቀሳቀስና ዘመናዊ ሳይንሳዊ ምርምሮች የሚካሄዱበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የህክምና ሙያ በምርምር መታገዝ አለበት ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ ደረጃውን በጠበቁ የምርምር መሳሪያዎችና የላብራቶሪ ዕቃዎች የተሟላው ማዕከሉ፤ ዩኒቨርስቲው እየሰጠ ያለውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶች ለማገዝና በህክምና ሙያ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት ያግዛል ብለዋል፡፡
በማዕከሉ በተለይም በቆላ በሽታዎችና (ካላዘር፣ የቆዳ በሽታና ወባ) በጉበት በሽታ ላይ ትኩረት ያደረገ ምርምር የሚካሄድ ሲሆን እንደኤችአይቪ ፣የሳንባ ነቀርሳና ሌሎች ተያያዥ በሽታዎችን በተመለከተም ምርመራና ጥናት እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
የአሰላ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም በአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስር ተቋቁሞ በጤና ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎችን እየተቀበለ የሚያሰለጥን ሲሆን ከመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞች መካከል 90 የሚሆኑትን በቅርቡ አስመርቋል። በአሁኑ ወቅት አንድ ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ፕሮግራሞች ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ የሚገኝ መሆኑም ተገልጿል፡፡

Published in ዋናው ጤና
Saturday, 19 October 2013 11:57

“ልብ አድርጉልኝ…”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ ዝም የሚል ሰው አለ። የማያውቅ ሆኖ ዝም የሚልም አለ፣ እያወቀ ጊዜ እስኪያገኝለት የማይናገርም አለ፡፡” ይቺ አባባል ከታላቁ መጽሐፍ ላይ የተገኘች ነች፡፡
እናላችሁ…ነገርዬው ሁሉ ጭጭ ምጭጭ ያለ አይመስላችሁም! ሰዋችን ‘ዝም’ ብሏል፡፡ ታዲያማ…ዝም ማለት ግን ነገሩ ሁሉ ‘አልጋ በአልጋ’ ስለሆነ… ህይወት ‘ዓለም ዘጠኝ’ ስለሆነች… “እሰይ ስለቴ ሰመረ…” የሚባልለት ዘመን ስለመጣ ምናምን አይደለም፡፡ ሰዋችን…አለ አይደል…ዝምም ብሎ ድምጽ ሳይወጣውም፣ “ያዙኝ ለቀቁኝ” እያለ ለያዥ ለገናዥ ሳያስቸግር፣ ደረቱን ሳይደልቅ፣ ፊቱን ሳይቧጭር፣ ጸጉሩን ሳይነጭ… በሙሉ ጸጥታም “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
እንግዲህ ጨዋታም ጨዋታ ያነሳው የለ…ለምን እንደሆነ እንጃ እንጂ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…እዚህ አገር…አለ አይደል… ከዕድር ዳኝነትና ዕቁብ ሰብሳቢነት ጀምሮ ያሉ ‘ወንበሮች’ ሁሉ የ“እኔ ከሞትኩ…” ምናምን አይነት ሶፍትዌር የተገጠመላቸው ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ… አንዳንድ ቦታ የምናየው እብሪት ቀላል ነው እንዴ! (“እኛም አንድ ሰሞን እንዲሀ አድርጎን ነበር…” የሚለው ነገር የሞባይል ‘ኮምልሰሪ ሪንግቶን’ ይሁንልንማ! የምር እኮ…አለ አይደል… “ለእኛ የተደረገውን እጥፍ ለሌላው ያድርግለት…” አይነት ነገር የሚል ‘ባለ ወንበር’ እየናፈቀን ነው፡፡ እናላችሁ…“በጥፍሬም፣ በጥርሴም ወንበሬን አላስነካም…” ባይ ሲበዛበት ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ክፋቱ ምን መሰላችሁ…መጀመሪያ ሲቀመጡበት ስፖንጅ በስፖንጅ የነበረው አንዳንድ ወንበር ሳይታሰብ ‘አስፈንጥሮ ሲጥል’ እንጂ ‘አስፈንጣሪ ስፕሪንግ’ እንዳለው የሚታወቀው ኋላ መሆኑ!
ደግሞላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አይደለም የአገሩንና የዓለምን ታሪክ ሊያነብ…አለ አይደል…የ‘ተንኮለኛው ከበደን ታሪክ’ እንኳን የማያውቅ የእኔ ቢጤ “ፍየል ከመድረሷ…” በአገር ታሪክ ሲሳለቅ፣ እንደ ወር ወጪው የአገርን ታሪክ ቁጥር ሲቀንስና ሲያቀናንስ… ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ደምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ሌላ ደግሞ አለላችሁ…ነገ አልመች ሲለው ትቶ ውልቅ የሚለው፣ ነገ የሚሰጠው ድርጎ ሲያንስበት ከፍ አድርጎ ድርጐ ለሚሰጥ ሌላ ጌታ ለማገለገል በጨረታው የማይገደደው…አሁን “የምናምኖች መጠራቀሚያ…” እያለ ወደሚሰደድባት አገር ‘ሽል’ ብሎ ወይ የሚነግድ ወይ ምናምኖች ሲላቸው የከረማቸውን “ፉርሽ ባትሉኝ…” የሚለው ሁሉ…አለ አይደል…“ታራለህ ትደብናለህ፣ ታዲያ ምን አባክ ትሆናለህ…” አይነት ማን አለብኝነት ኑሮውን የምድር ገሀነም ሲያደርግበት… ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ከአንድ ጥግ አንድ ጥግ እንደ ኳስ ሲያጦዙት ከርመው…ሣር የነበረላቸው ነገር ወደ ድርቆሽ መለወጥ ሲጀምር ሽል ሲሉ… ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
እናላችሁ…እንደ ትናንትና፣ እንደ ትናንት ወዲያ አገር “የባለ አገሯ…” መሆኗ እየቀረ እምነቱ ላይ ሲዘባበቱበት፣ የከበረ ባህሉ ላይ በ‘ግሎባላይዜሽን’ና ‘ወዳጆችን ባለማስቀየም’ ሰበብ ለሚጠየፋቸው ልማዶች እንዲጋለጥ ሲያደርጉት፣ በእሱነቱ ‘ሙድ ሲይዙበት’ (ቂ…ቂ…ቂ…)…ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ስሙኝማ፣ እግረ መንገዴን የሆነች ነገር ትዝ አለችኝማ!…ምንም እንኳን ወደየምግብ ቤቱ በሩብ ዓመትም ቢሆን ብቅ የሚያደርግ አቅም ከጠፋ ቢከራርምም አልፎ፣ አልፎ እንደ አቅሚቲ ያለውን ተጠግቶም ቢሆን ብቅ ማለት አይቀርም፡፡ ታዲያላችሁ እዛም “ልብ አድርጉልኝ!” የሚያስብል ነገር መአት ነው፡፡
ታዲያማ…ሀሳብ አለን፣ አንዳንድ ምግብ ቤት በር ላይ የድንጋይ መፍጫ ማሽን ይቁምልንማ! አሀ…ልክ እኮ ‘ሞቶም ችኮነቱ ያልለቀቀው’ በሬ… “መንጋጋህ ይድከመው እንጂ በቀላሉማ ታፋዬን አታኝካትም…” የሚል ይመስል የሚታኘክ ሳይሆን የሚፈጭ ሥጋ እየቀረበልን ተቸገርና!
እናማ…የድንጋይ መፍጫ ‘ስታንድባይ’ ይሁንልን፡፡ ልክ ነዋ… እንደ ‘ፉድ አምቡላንስ’ ነገር ሆኖ ሊያገለግለን ይችላላ! የምር እኮ…አንዳንድ ጊዜ ከወጡ ውስጥ በመከራ ጠልፋችሁ የጎረሳችሁት ቁራጭ ሥጋ አፋችሁ ውስጥ ሦስት መቶ ስድሳ ዲግሪ አሽከርክራችሁትም ወይ ፍንክች! “ይሄ ሥጋ ከየትኛው እንስሳ እንደተገኘ አንድዬ ይወቀው…” ብትሉ አይፈረድባችሁም፡፡ እኔ የምለው… የሀበሻ በሬዎች እንደ እኛ የሀበሻ ሰዎች ነገራቸው ሁሉ መነቸከ ማለት ነው!
ስሙኝማ…እዚህ አገር “ልብ አድርጉልኝ!” የሚያስብል ነገር እንዴት እንደበዛ የምታወቁት ምን የመሰለው ሬስቱራንት ውስጥ የምግባችሁን መቅረብ3 ተከትሎ እግራችሁ ስር የስፔንን ተዋጊ ኮርማዎች የሚያስንቅ ድመት ብቅ ብሎ ይገላምጣችኋል! “እኔ እዚህ ቅንጣቢ የሚጥልልኝ አጥቻለሁ አንተ ገንዘብ አለህና አሮስቶ ስትውጥ የድመት አምላክ አይታዘብህም!” ብሎ የሚዝትባችሁ ነው የሚመስለው፡፡…ነው ወይስ ሼፉ እንዲሰልል ልኮት ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
ታዲያላችሁ… እንግዲህም ጨዋታም አይደል… “ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል…” የሚለውን አባባል የሚያረጋግጡ፣ “ጌታዋን የተማመነች በቅሎ…” የሚለውን አባባል እውነት የሚያደርጉ፣ ላላስነጠሰው ባለስልጣንና ባለሀብት መሀረብ የሚያቀርቡ እህል እንደሚፈጅ ተምች በዙሪያው እየፈሉ ሲሄዱ… ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
በዕውቀትና በ‘ሜሪት’ ስልጣን ሳይሆን…በ‘ድርጎ ስልጣን’ ለዓይንም መከታተል በሚያስቸግር ፍጥነት ወደላይ እየተተኮሱ…የመንግሥተ ሰማያትን ዙፋን የተቆጣጠሩ ይመስል አይደለም ሌላ ሌላውን… የተፈጥሮ መብቶቹን እንኳን ሰጪና ነጣቂ ሲሆኑበት ….ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
“ይህንን ብታደርግ በዚህና በዚህ እናግዝሀለን…” ከማለት ይልቅ…“ይሄን ብታደርግ ውርድ ከራሴ…” አይነት “መች ተዋጋና ገና ነው ገና…” ማለት የሚቃጣቸው ግለሰቦችና ተቋማት ሲበዙበት “መሽናት ክልክል ነው” ከሚል ይልቅ “ትሸናና ትሸነሸናነህ!” የሚሉ ሚጢጢ ጉልበተኞች እየበዙ ሲሄዱ፣ መመሪያዎች፣ ዘጋቢ ፕሮግራሞች ምናምን… “ፈቀድን!” ከሚለው ይልቅ “ከለከልን!” ወደሚለው ትርጉም ሲያዘነብሉ…ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ስንትና ስንት የሚያኮሩ ልምዶችና እሴቶች እንደ ሌሉት ሁሉ… “ከእከሌ የወሰድነው…” “ከእነ እከሌ የቀዳነው…” እየተባለ የ‘ፈረንጅ ፍርፋሪ’ ለቃሚ ሲያስመስሉት…ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
በ‘አፈ ቅቤውም’ በ‘አፈ ኮምጣጤውም’ የዘለፋ ናዳ የሚወርድባቸው የቀድሞ ዘመን ነገሥታት… አለ አይደል… “ሁሉንም ነገር አደረግናላችሁ፣ አፈራችንን ግን ይዛችሁ አትሄዱም…” አይነት ነገር እያሉ ጫማ እያሳጠቡ መርከብ ላይ እዳላሳፈሩ ሁሉ…ዛሬ በየቦታው ‘ቅድሚያ ለነጭ’ አይነት ነገር እየበዛበት፣ ጭርሱን “ለፈረንጅ ጫማውን ብታብጥለትስ ምን አለበት…” ሊባል ምንም ያልቀረን ሲመስል…ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
አንዳንድ ቦታ በችሎታ ሳይሆን በመጠሪያ ስሙ ብቻ ማንነት ‘እየተበጀለት’ ብቁ ለሆነበት ቦታ ሁሉ “ብቁ አይደለህም…” ሲባል፣ በሠለጠነበትና የሥራ ልምድ ባካበተበት ቦታ ሳይሆን…አለ አይደል… በተወለደበት ስፍራ ሲመዘን… ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የስም ነገር የምር አስቸጋሪ ነው። ምን መሰላችሁ…አንዳንድ እዚቹ አገር በሚገኙ ስፍራዎች አገልግሎት ለማግኘት ስም እስከ አያት ድረስ ይጠየቃል የሚባል ነገር አለ፡፡ መቼም ጉዳችን ተወርቶ አያልቅ!
እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝ… አንድ ጊዜ አንድ በ‘ተጨማሪ ሰዓት’ ሊንቀሳቀስ እየተቃረበ የነበረ ወዳጄ የሆነች እንትናዬ ላይ…በትኩሶቹ ቋንቋ… ‘ጆፌ ጥሎ’ ሲያንዣብብ ይከርምና ሊሳካለት ጫፍ ይደርሳል፡፡ ታዲያላችሁ…ይሄን ሁሉ ጊዜ የሚያውቀው ዋናውን ስሟን ሳይሆን ‘ባክአፕ’ መጠሪያዋን ነው፡፡
ታዲያላችሁ…አንድ ቀን እውነተኛ ስሟ ከሦስተኛ ወገን ይነገረዋል፡፡ መጥቶ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው…“አንተ ያቺ እንትና ስሟ እንትና ነው እንዴ!” አለላችሁና…በቃ የፕሮጀክት ትግበራውን አቆመዋ! እዚህ ደረጃ መድረሳችን በጣም አያሳዝንም!
ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” የሚያስብሉት ነገሮች የሚቀንሱበትን ዘመን አንድዬ ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Page 6 of 16