በአዲስ አበባ በየዓመቱ የሚካሄደው የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል ትላንት ዕለት ምሽት በ12 ሰዓት በጣልያን የባህል ማዕከል The Great Beautiful በተሰኘው የጣልያን ፊልም ተከፈተ፡፡
ለ15 ቀናት በሚዘልቀው የፊልም ፌስቲቫል ላይ የ15 አውሮፓ አገራት ፊልሞች ለተመልካች የሚቀርቡ ሲሆን የጣልያን ባህል ማዕከልን ጨምሮ በገተ ኢንስቲቲዩትና በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ፊልሞቹ እንደሚታዩ ታውቋል፡፡
ሁሉም ፊልሞች በነፃ ለተመልካች የሚቀርቡ ሲሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወይም በእንግሊዝኛ ትርጉም (subtitles) እንደተዘጋጁም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፊልም ፌስቲቫሉ ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም The Selfish Giant በተሰኘው የእንግሊዝ ፊልም እንደሚጠናቀቅም ታውቋል፡፡

Monday, 06 October 2014 08:41

“መረቅ” ነገ ይመረቃል

በደራሲ አዳም ረታ የተጻፈው “መረቅ” የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የደራሲው አድናቂዎችና የጥበብ ቤተሰቦች በተገኙበት ነገ ጧት በሃገር ፍቅር ቲያትር አዳራሽ ይመረቃል፡፡
ለረጅም አመታት በውጭ አገራት የኖረው ደራሲ አዳም በሚገኝበት በሚከናወነው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ፣ የተለያዩ ስነ-ጽሁፋዊ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ስለደራሲው ስራዎችም ማብራሪያ ይሰጣል፡፡
ለደራሲው ስምንተኛ ስራው የሆነውና 600 ገጾች ያሉት “መረቅ”፣ በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን የመሸጫ ዋጋውም  120 ብር ነው፡፡

           በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ሲኒማ ቤቶች በስፋቱ ትልቅ የሆነውን ፐርፎሬትድ ስክሪን ያስገጠመውና በዘመናዊ መልኩ የተደራጀው “ክሊንገር ሲኒማ”፣ አዳዲስ አገረኛ ፊልሞችን በመሳየት አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
“ክሊንገር ሲኒማ” በተለይ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ እንዳለው፣ በአዲስ አበባ ልደታ ኮንዶሚኒየም አካባቢ በሚገኘው መኮንን ቢተው ህንጻ ላይ የተከፈተውና በየዕለቱ በ8፣ በ10 እና በ12 ሰዓት በሶስት ፈረቃ ፊልሞችን ማሳየት የጀመረው ሲኒማ ቤቱ፣ በከተማዋ በስፋቱ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ ፐርፎሬትድ ስክሪን ያለው ሲሆን፣ 7.1 ሰራውንድ ሳውንድ ሲስተም የተገጠመለት ነው፡፡ በዘመናዊ መልኩ የተደራጀና የሙቀት መቆጣጠሪያ የተገጠመለት የፊልም አዳራሽ፣ 400 ተመልካቾችን የሚያስተናግዱ ምቹ ወንበሮችና ጥራታቸውን የጠበቁ ተጨማሪ 40 የቪአይፒ ወንበሮችም አሉት፡፡ሲኒማ ቤቱ ለትራንስፖርት ምቹ በሆነ ቦታ ላይ እንደሚገኝ፤ ንጹህና በቂ የእንግዳ ማረፊያ፣ ዘመናዊ ካፌና ሬስቶራንት እንዲሁም አስተማማኝ ጥበቃ ያለው በቂ የመኪና ማቆሚያ እንደተሟላለትም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

በደራሲ አብነት ስሜ የተጻፈውና ከዚህ በፊት ለንባብ የበቃው “የኢትዮጵያ ኮከብ” የአስትሮሎጂ መጽሃፍ ቀጣይ ክፍል የሆነው  “ፍካሬ ኢትዮጵያ” ከነገ በስቲያ ጀምሮ በገበያ ላይ ይውላል፡፡ 404 ገጾች ያሉት “ፍካሬ ኢትዮጵያ” የ12ቱ ኮከቦች ሐተታ በ1,200 ስመጥሮች ዝርዝርና በበርካታ ሀገራዊ ምሳሌዎች ታግዞ የቀረበበት ሲሆን፣ ትውፊትን በማኄስ ምርመራ የዐውደ ነገሥት ተወዳሽ እና ተወቃሽ ጐኖችን ይፈትሻል፡፡
መጽሃፉ ልቦለድን በአስትሮሎጂ ማእቀፍ ውስጥ በመተርጐም ሙከራ፣ የ“ፍቅር እስከ መቃብር” የረጅም ልቦለድ መጽሃፍን ገፀ-ባህርያት ኮከብ እና ውክልና የሚቃኝ ሲሆን፣ የታዋቂ ሰዎችን ጉልህ ስብእና በልደት ሰንጠረዥ አማካይነት ተተንትኗል። የኢትዮጵያንና የአስትሮሎጂን፣ የቃላትንና የከዋከብትን፣ የጨረቃንና የሥነ ተዋልዶን ልዩ ተዛምዶም ይዳስሳል፡፡“ፍካሬ ኢትዮጵያ” ከሰኞ ጀምሮ በአዟሪዎችና በመጽሃፍት መደብሮች በ70 ብር ከ80 ሳንቲም ይሸጣል፡፡

በኢትዮጵያ የሴቶች ማህበራት ቅንጅትና በአጋር ድርጅቶቹ አማካይነት የታተመውና ከ60 በላይ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ታሪክ የያዘው “ተምሳሌት - እጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች” መጽሃፍ የፊታችን ማክሰኞ አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም ይመረቃል፡፡
ከ300 በላይ ገጾች ያሉት መጽሃፉ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን፣ የአማርኛው ቅጽ 20 ሺህ ኮፒ፣ በመላ አገሪቱ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የሴቶች ክበባት፣ በሴቶች ዙሪያ ለሚሰሩ ቡድኖችና ድርጅቶች በነጻ ይከፋፈላል ተብሏል፡፡ዋና አዘጋጇም አሜሪካዊቷ ሜሪ ጄን ዋግል ናት፡፡

Monday, 06 October 2014 08:35

ዜማ ቤት

ድጉዋ ጾመድጉዋ
“ዜማ የመጣው ከመላዕእት ነው፡፡ ዜማ፤ ታላቅ፣ ከፍ ያለ ማለት ነው፡፡” ይላሉ መሪጌታ ግሩም ዮሃንስ የባህር ዳር ጊዮርጊስ የድጉዋ መምህር፡፡ ለዚህ አባባላቸው ማስረጃ ናቸው ያሉዋቸውን የቅዱስ ያሬድ ጥቅሶች አቅርበዋል፡፡ “አቢይ ዜማ ተሰምአ በሰማይ፡፡ ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ” (ትልቅ ዜማ በሰማይ ተሰማ፤ በሰማይ የሰማሁት ዜማ ወይ ዜማ!)” ሲሉ፡፡
በሌላም በኩል የሞጣ ጊዮርጊስ ዜማ መምህር የሆኑት መሪጌታ ቀለሙ አድገህ፤ “ዜማ ህዝበ ክርስቲያንን በተመስጦ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ጣፋጭ ጎዳና ነው” ይላሉ፡፡
የሆነ ሆኖ ዜማ ተሰጥኦ ባላቸው ካህናት ሲዜም የምዕመናኑን ልብ መመሰጡ፣ ከንፈር ማስመጠጡ የተለመደ ነው፡፡ በተለይ “አራራይ” የተባለው ዜማ እንኩዋን ምዕመኑን ሌላውንም ቢሆን የመሳብ አንዳች ሃይል እንዳለው ጠበብቱ ይመሰክራሉ፡፡
ዜማ በድምጸ መረዋ ሊቃውንት ሲዜም ከረጅም ጥልቀት ዘልቆ የሚደመጥ ህሊና የሚነሽጥ መሆኑን የአፄ ካሌብ 3ኛ ልጅ አፄ ገ/መስቀል ሳይቀሩ በዘመናቸው ለነበረው ቅዱስ ያሬድ መስክረዋል፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት ያሬድ ከአፄ ገ/መስቀል (የዘመኑ ንጉስ ከ515-529 ዓ.ም) ፊት ቆሞ በጥኡም ልሳኑ ዜማውን ሲያንቆረቁር፣ ንጉሱ ህሊናቸውን ስተው የያሬድን እግር በጦር እንደወጉት ይነገራል፡፡
ያሬድ ዜማውን ፈጥሮ እሱ ቀምሮ፣ ዘምሮና አንጎራጉሮ አልቀረም፤ ጉባኤ ዘርግቶ፣ ስርአት አበጅቶ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ለእነ ሳዊራ፣ ለነ አባ ጌራ አስተማረ እንጂ፡፡ እነሱም ከያሬድ የተረከቡትን ታላቅ አደራ ለልጆቻቸው አስተላልፈዋል፡፡ በዚህ ሂደት የዜማ፣ ፈላጊው ቁጥር እያደገ ሲመጣ የትምህርት ቤቱም መጠሪያ ዜማ ቤት ሆነ፡፡
ዜማ ቤት የቃል ትምህርትን (የሌሊት ትምህርትም ይሉታል) ጨምሮ ጾመ ድጉዋና ሌሎችም የዜማ ትምህርቶች ይስተናገዱበታል፡፡ ጾመ ድጉዋም ሆነ ድግዋው በያሬድ የተደረሰ መሆኑን ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡ የሚዜመውም እንዲያው በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ለእያንዳንዱ ቃል በያሬድ የተቀረጸ ህግና ደንብ አለው፤ የዜማ ምልክትና የዜማ አይነት፡፡
ወደ ዜማ አይነቶችና ምልክቶች ከመግባታችን በፊት ድጉዋ ምን ማለት እንደሆነ እስኪ በጥቂቱ እንመልከት፤ መሪ ጌታ ግሩም ዮሃንስ ለድጉዋ ሶስት ትርጉም ይሰጡታል፡፡
1ኛ. “ደጉአ ማለት ጻፈ ሲሆን ድጉዋ የተጻፈ የተደረሰ ማለት ነው፡፡
2ኛ. “ደጉአ በሃማሴን የለቅሶ ጥሪ ነው፤ ያሬድም በዚህ ድርሰቱና ዜማው አልቅሶ ፈጣሪውን ለምኖበታል፤ አመስግኖበታል፡፡
3ኛ. “ድግዋ ሲላላ የቤተ ክርስቲያን ትጥቅዋ ማለት ነው” በማለት፡፡ ከዚህ ሃሳብ በመነሳት ስንመለከተው ለድግዋ የተሰጡት ሶስቱም ትርጉሞች ትክክል ይመስሉናል፡፡ ድግዋ በኢትዮጵያዊ ቋንቋ ተደርሶ ባገርኛ ኖታ ተወስኖ የቤተ ክርስቲያንን ወገብ አጥብቆና አድምቆ የኖረና የሚኖር ለመሆኑ እማኝ የሚያሻው አይደለም፡፡
ከአፍሪካ ህዝቦች የራሳችን ፊደል ያለን ብቸኛ የስነ-ጽሑፍ ባለሀብቶች ነን ስንል በዋቢነት ከምናቀርባቸው በርካታ ቅርሶች አንዱም ይኸው ድጉዋ ነው፡፡ በዜማ ቤት ታላቅ ክብር የሚሰጠው በመሆኑም የድጉዋ ተማሪዎች ሳይቀሩ በስሙ ይኮሩበታል፡፡
ድጉዋን “መሃረ” ብሎ ማዜም የጀመረ ተማሪ ከልመና ስቃይ ይገላገላል፤ ለምነው የሚያበሉት ከእሱ በታች ያሉት የዜማ ደቀ መዛሙርት ናቸውና! በመሆኑም በዜማ ቤት እንኳን ድግዋ የድጉዋ ተማሪው ልዩ ክብር ስላለው ካህናት ያሞግሱታል፤ ምእመናንም ያደንቁታል፡፡
ተሜ ከብረትና ከቆዳ ወይም ከቀርቀሃ በተሰራው አትሮኑስ ላይ ዘርግቶ ድጉዋን ሲያናግረው እንደ ምንጭ ውሃ ሲያንቆረቁረው እውነትም ከአምላኩ ጋር ህቡእ ስለሆነው ዓለም የሚነጋገር ይመስላል፡፡
በዜማ ቤት ብዙ አስደናቂ ሁኔታዎች ቢኖሩም የመምህሩ ጉዳይ በተለይ መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ ቁጥሩ በርካታ የሆነ ተማሪ ዙሪያቸውን ከቦ የእሳት ቃጠሎ የተነሳ ይመስል ሲብላላ የሁሉንም ጩኸት (ለትምህርት ነው) በጥንቃቄ እያዳመጡ “እገሌ ምልክቱን ስተሃል፣ አንተኛው ዜማውን አወላግደሃል… ወዘተ” በማለት የሚሰጡት እርማት ከበርካታ ሙዚቀኛ መሃል ልክ ያልሆነውን ለይቶ የሚያስተካክልና የማዳመጥ ችሎታው ከፍተኛ የሆነ የሙዚቃ መሪ ያስመስላቸዋል፡፡ ዜማው የሚዜመው “ግዕዝ፣ እዝልና አራራይ” በሚባሉ የዜማ ስርአትና ልክ ነው፡፡ ተማሪው ከዚህ ስርአት እንዳይዛነፍ የመጣበት ኃላፊነት አለባቸው፡፡
“ግዕዝ፣ እዝልና አራራይ” ለተባሉት የዜማ አይነቶችም ሊቃውንቱ የሚከተለውን ትርጉም ይሰጣሉ፡፡
“ግዕዝ ማለት ርቱዕ /ቀና ልጁን አሳልፎ የሚሰጥ አብ፣ እዝል ጽኑእ /ጠንካራ ወልድ፣ አራራይ አራህራሂ/ አሳዛኝ ጥዑም መንፈስ ቅዱስ/ ነው” በማለት በአብ በወለድና በመንፈስ ቅዱስ ይመስሉዋቸዋል፡፡
በሶስት አይነት አዚያዚያም የተዘጋጀው ድጉዋም ሆነ ሌላ የዜማ ትምህርት በውሱን ምልክቶች ይዜማል - “ድፋት፣ ቅናት፣ ይዘት፣ ደረት፣ ጭረት፣ ርክርክ፣ ድርስ፣ አንብር፣ ሂደት፣ ቁርጽ” በሚባሉ፡፡ ከእዚህ ሌላም የዘር ምልክቶች እንዳሉ ሊቃውንተ ዜማ ይናገራሉ፡፡ እኒህ ግን ቀዋሚ ምልክቶች ናቸው፡፡
አንድን ቃል በሶስት በአራት ምልክቶች ማዜምም ይቻላል፡፡ ይህ ታዲያ አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ሲሆን ስሙም “ጠንቀቅ” ይባላል፡፡ አንዳንድ መምህራን ግን “አመል” ይሉታል፡፡ የዚያ ቃል የአዚያዚያም ልዩ አመል መሆኑ ነው፡፡ ልዩ ስለሆነም ነው “ጠንቀቅ” የተባለው፡፡ ድጉዋ በሶስትም በአራትም ይከፈላል፡፡ ለምሳሌ ቀኝ ጌታ አንተነህ ጥሩነህ ቀራንዮ መድኀኔዓለም የዜማ መምር “ድጉዋው በአራት ይከፈላል፤ ጾመ ድጉዋ፣ አስተምህሮ፣ ዮሃንስ፣ ፋሲካ በሚባሉ” ሲሉ፤ መሪጌታ ወርቄ አያሌው የተባሉ የቆሜ አብነት መምህር እና መሪጌታ ግሩም ዮሀንስ የቤተልሄም መምህር ደግሞ “ድጉዋው በሶስት ይከፈላል፤ አስምህሮ፣ ፋሲካ፣ ዮሃንስ በሚባሉ” ይላሉ፡፡ አንድ የሚያስማማቸው ነጥብ ግን አለ፡፡ ድጉዋ በሶስትም ይከፈል በአራት የተደረሰው በቅዱስ ያሬድ መሆኑን ሁሉም ያምኑበታል፡፡ ›
ሌላም ነገር አለ፤ “ትበሃል” የሚባል፡፡ የዜማ ጠበብት በአዚያዚያም /ይትበሃልም ይሉታል/ ይለያያሉ፡፡ ልዩነታቸውም በምልክት ወይም በዜማ አይነት አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድን ቃል በማጥበቅና በማላላት የተለያዩ ትርጉም ማግኘት እንደሚቻል ሁሉ ዜማውንም ከፍ፣ ዝቅ ወሰድ፣ መለስ፣ ዝግ፣ ፈጠን… በማድረግ የአዚያዚያም /አጩዋጩዋህ/ ልዩነት ማወቅ ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ዜማ “ቤተልሄም፣ ቆሜ፣ አጫብር፣ ወንጨር፣ ተጉለቴ” በሚባሉ ይትበሃሎች ይከፋፈላል፡፡
የዜማ ደራሲው ቅዱስ ያሬድ ሆኖ ሳለ እንዴት በአምስት ዜማ (ይትበሃሎች) ሊከፋፈል እንደቻለ የድግዋ ሊቃውንቱ “ለክፍፍሉ ምክንያት የግራኝ አህመድ ጦርነት ነው” ይላሉ፡፡ ቅድመ ግራኝ ዜማው በአንድ አይነት ዜማ ይዜም ነበር፡፡ በጦርነቱ ወቅት አያሌ ካህናት ሲያልቁ የዜማ መጻህፍትም እንዳልነበረ ሆነዋል፤ ተቃጥለዋል፣ ተዘርፈዋል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ከሞት የተረፉ ካህናት ከየተሰወሩበት እየወጡ ድጉዋውን ማዜም ሲጀምሩ፣ የአዚያዚያም ልዩነቶች ተከሰቱ፤ ካህናቱም “የእኔ ነው ልክ” የሚል ፉክክር ጀመሩ፤ ችግሩን ለመፍታት ሲባልም አስረጅ ተፈላጊ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ድጉዋውን ከቀበሩበት በማውጣት እማኝ ያቀረቡት ከጎንደር አካባቢ የቤተልሄምና ቆማ ፋሲለደስ፣ ከጎጃም የወንጨር ጊዮርጊስና የአጫብር አቦ፣ ከሰሜን ሸዋ የተጉለት ሊቃውንት ብቻ ናቸው፡፡ ይሁን እንጅ ቤተልሄምና “ቆማ” ከሚባለው ቃል ስያሜውን ያገኘው  ቆሜ አብነት /አስረጅ/ ሆኑና ተከታያቸው በዛ፤ እስከዛሬ ድረስም ለድግዋ መምህራን ምስክርነት ይሰጣሉ በድጉዋ ብቁ ለመሆናቸው የምስክር ወረቀት ሰጥተው ያስመርቃሉ ማለት ነው፡፡
ይሁን እንጅ ሌሎችም /አጫብር፣ ወንጨርና ተጉለቴ ማስረጃ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ዓመቱን ሙሉ ባሉ ቀናት ልክ የተደረሰው የያሬድ ዜማ በአዚያዚያም ስልት ይለያይ እንጅ የትምህርት አሰጣጡ በሁሉም ዘንድ አንድ ነው፡፡ የቤተልሄሙ፣ የቆሜው፣ የአጫብሩ፣ የወንጨርና የተጉለቴው ተማሪ በሚማርበት ዜማ ቤት ውስጥ ከመዝሙረ ዳዊት ቀጥሎ እንዲማር የሚደረገው ጾመ ድግዋን ነው፡፡
ጾመ ድግዋው የሚያገለግለው በሁዳዴ ጾም ጊዜ ብቻ ስለሆነ “የጾም ድግዋ” ተብሎዋል፡፡ ይህን የጾም ድግዋ ተሜ “ዘወረደ አምላእሉ፣ አይሁድ ሰቀሉ፣ እግዚአ ኩሉ ዘየሃዩ በቃሉ” /ከላይ የወረደውን፣ በቃሉ የሚያድነውን የሁሉን ጌታ አይሁድ ሰቀሉት/ ብሎ ሲጀምር ግራ መጋባቱ አይቀርም፡፡ ምልክቱ፣ አይነቱና ይትበሃሉ በአንድ ቀን ጀንበር አይያዝምና!
በግእዝ፣ በእዝልና በአራራይ፣ እያዘመ ምልክቶችን በየጊዜው እየደጋገመ ሲሄድ ግን ተሜ ከጾመ ድግዋው ጋር እየተላመደ ስለሚሄድ የዜማው መንገድ እየቀለለለት ትምህርቱ እየተገለጠለት ሆሳእና ድረስ ይዘልቃል፡፡ ሆሳእና የጾሙ ሳምንት መጨረሻ ስለሆነ ጾመ ድግዋውም በሆሳእና ሳምንት ማብቂያ በሚዘመረው “ክርስቶስ ተንስአ እሙታን” /ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ/ በሚለው መዝሙር ይጠናቀቃል፡፡
በዜማ ቤትም ሆነ በሌሎች የቤተ ክህነት ትምህርት ቤቶች ሁዳዴ (አርባ ጾም) በሚጾምባቸው ሁለት ወሮች ያሉት ሳምንታት ልዩ ልዩ ስያሜዎች አሉዋቸው፡፡ “ቅድስት፣ መጻጉእ፣ ደብረ ዘይት፣ ገብርሄር፣ ኒቆዲሞስና …” ሌሎችም፡፡ በእኒህና በሌሎች ባልጠቀስናቸው ሳምንታት ስያሜዎች መሰረት ነው ተሜ የተዘጋጀለትን ጾመ ድግዋ አዚሞ እንዲጨርስ የሚገደደው፡፡
እያንዳንዱዋን መዝሙር እየደጋገመ ሲያዜም ስህተቱን እየንታ (መምህሩ) እያረሙት እየተቀበለ ደጋግሞ ሲያዜም ይቆይና በዜማው ህግና ደንብ መሰረት ወደሚቀጥለው እንዲሻገር መምህሩ ሲፈቅዱለት ቀጣዩን ዜማ ያዜማል፤ ያውቃል፣ ያልፋል፡፡ በዜማ ቤት ካንዱ ትምህርት ወደ ሌላው ለመሸጋገር እንደ ዘመናዊ ትምህርት ፈተና አያስፈልግም ለተማሪው የሚቀርብለት ፈተና ማወቅ ብቻ ነው፡፡ ከላወቀ ግን በአንድዋ ትምህርት ይከርማታል እንጅ የጀመረውን በተገቢ ሁኔታ ሳያጠናቅቅ በይሉኝታ ብቻ ሊያልፍም ሊታለፍም አይችልም፡፡ በዜማ ቤት፣ ከጎበዝ ተማሪዎች መማር እንጅ መኮረጅ አይቻልም፡፡ ትልቅ ነውርም ነው “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ይባል የለ!? የማንም ጥገኛ ሳይሆን በማንም እውቀት ሳይኮራ በልመና ቁራሽ (ኮቸሮ) እየተሰቃየ ተሜ ጾመ ድግዋውን ከጨረሰ በኋላ ወደ ድግዋ ይሸጋገራል፡፡ ድግዋ የጾመ ድግዋ ታላቁ ክፍል እንደ መሆኑ ትምህርቱ ሰፊ ይሁን እንጅ የሚዜመው ግን ቀደም በጠቃቀስናቸው የዜማ አይነቶችና ምልክቶች ነው፡፡ ድግዋው ታዲያ “ጠንቅቅ” የሚባል አመል ያለው መሆኑና በሶስት ዘመናት መከፋፈሉ ታላቅነቱን ከማስመስከሩም በላይ እንደ ጾመ ድግዋው በአጭር ጊዜ የሚያልቅ አይደለም፡፡ መቸም ይለቅ መቸ ተሜ የጀመረውን ሳይጨርስ ወደ ሁዋላ እንደማይል መምህራኑ ይናገራሉ፡፡
ከዘመኑ ተማሪ ጋር ሲነጻጸር የዜማ ቤቴ ተሜ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ጥንካሬ እንዳለው ከኑሮውና ከትምህርት ፍላጎቱም ማወቅ ይቻላል፡፡ የወፍ ጎጆ በምትመስለው ውትፍትር ቤት ውስጥ እየኖረ የቀን ሃሩር የሌሊት ቁር ሳይበግሩት የቀን ጃኬቱ የሌሊት ብርድ ልብሱ በሆነችው ደበሎው ብቻ ተወስኖ፤ የዘመኑ ፋሽን ልቡን ሳያማልለው ወጣትነቱ ለተልካሻ ተግባር ሳይሸነግለው ለተሰማራበት መስክ ብቻ ሽንጡን ገትሮ ሃሞቱን ኮስትሮ ይታገላል፡፡ ትግሉም እንዲሁ አይቀርም፤ ፍላጎቱ በጠንካራ ጥረቱ ይሳካል እንጅ!  እንዲህ ሲባል ዜማ ቤት የገባ ሁሉ ድግዋ ይማራል፤ ይፈጽማል ማለት አይደለም፡፡ ከጾመ ድግዋ ላይ ትምህርቱን አቁዋርጦ ሚስት ከሚያገባው፣ ወደ ቅኔ ቤት ከሚሄደው ሌላ ድግዋ ራሱ የሚጠምመውም አይጠፋም፡፡ አንዳንዴ ትምህርት አልሳካልህ ሲለው በጆሮ ጠጋብነት የሰማውን ከዚያም ከዚያም በመጠቃቀስ ሊቅ ለመምሰል ሲሞክር “ጥራዝ ነጠቅ!” ይባላል፡፡ በልብስ ብቻ አዋቂ መሆን ለሚከጅለው ልብሰ ኩንስንስም “ልብሰ ተማሪ!” የሚል ቅጽል ስም ይወጣለታል፡፡ በየተማሪ ቤቱ በመንከራተት ብቻ እድሜውን የሚገፋውንም “እግረ ተማሪ!” ይሉታል፡፡ ከዚህ ሁሉ መሃል ነው እንግዲህ ጎበዞች ነጥረው የሚወጡት፡፡ ችግርን ተቋቁመው ቀለም አጣጥመው የእውቀቅ ሰዎች የሆኑትንም ህዝቡ “የቀለም ቀንድ!” ሲል ያሞካሻቸዋል፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በሁዋላ ለድግዋ መምህርነት ከበቁት መሃል ለአብነት መሪጌታ ግሩም ዮሃንስን መጥቀሱ ይበቃል፡፡ ባህር ዳር ጊዮርጊስ ውስጥ ድግዋ በማስተማር ላይ የሚገኙት እኒሁ ሊቅ ከድግዋ መምህርነት ማእርግ ላይ ለመድረስ ሃይ ሁለት አመት ፈጅቶባቸዋል፡፡ “ያሁኑ ተማሪ የተለመፀ ብራና ነው፣ በሊህ ነው!” ግን የዓላማ ጽናት የለውም፡፡ በእኛ ጊዜ ግን ጥንካሬያችን ትዕግስታችንና ጽናታችን ብቻ ነበር፡፡” በማለት እኒሁ ምሁር ያሁኖችን ከቀድሞዎቹ ጋር በማነፃፀር ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ካሰቡት ለመድረስ እንቅስቃሱ ሲጀመር ልዩ ልዩ መሰናክሎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ በቅድሚያ ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ችግሮችን አስቀድሞ ማወቅ ደግሞ መፍትሄ ለመፈለግ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም በላይ በጥረት ለውጤት መብቃትም ከፍተኛ የሆነ ህሊናዊ እርካታ መስጠቱ አያጠራጥርም፡፡ ለመሆኑ የዘመናችን ወጣቶች ከቤተ ክህነት ባለሙያዎች የሚማሩት ቁምነገር ይኖር ይሆን?

Published in ጥበብ
Monday, 06 October 2014 08:33

የፍቅር ጥግ

አንድ ወጣትና አንዲት ኮረዳ በሞተር ሳይክል ይጋልባሉ፡፡ ሞተሩ 100 ሜትር በሰዓት ይከንፋል፡፡
ኮረዳዋ፡- ቀስ በል በናትህ፤ በጣም ያስፈራል!
ወጣቱ፡- አይዞሽ፤ ደስ ይላል እኮ!
ኮረዳዋ፡- ምንም ደስ አይልም፤ በናትህ በጣም ነው የሚያስፈራው!
ወጣቱ፡- እንግዲያውስ እወድሃለሁ በይኝ፡፡
ኮረዳዋ፡- እሺ እወድሃለሁ፤ ግን ቀስ በል!
ወጣቱ፡- በይ ሄልሜቴን ውሰጂና ጭንቅላትሽ ላይ አጥልቂው፤ እኔን አስጨንቆኛል፡፡
በነጋታው በወጣ ጋዜጣ ላይ፡- አንድ ሞተር ሳይክል ፍሬን በጥሶ ከአንድ ህንፃ ጋር በመጋጨቱ ሞተሩ ላይ ከነበሩት ሁለት ሰዎች አንደኛው ህይወቱ ወዲያው አልፏል፡፡ የሆነው እንዲህ ነው፡- ጥንዶቹ ግማሽ መንገድ እንደከነፉ፣ ፍሬኑ እምቢ ማለቱን ወጣቱ ተገንዝቧል፡፡ ነገር ግን ፍቅረኛው ይሄን እንድታውቅ አልፈለገም፡፡
ይልቁንም ለመጨረሻ ጊዜ እወድሃለሁ የሚለውን ጣፋጭ ዜማዋን ማዳመጥ ስለፈለገ እንድትልለት ጠየቃት፡፡ ከዚያም ሄልሜቱን (ከአደጋ መከላከያውን) ከራሱ ላይ ወስዳ እንድታጠልቀው አደረጋት፡፡
ወጣቱ ሄልሜቱን ባለማድረጉ ለሞት እንደሚዳረግ ያውቅ ነበር፡፡ እሱን ያሳሰበው ግን የፍቅረኛው ህይወት ነው፡፡ ስለዚህም እሱ ሞቶ፤ እሷን አተረፋት፡፡  

Published in የግጥም ጥግ
Monday, 06 October 2014 08:32

የፀሐፍት ጥግ

ስለፖለቲካ

ፖለቲካ በጣም ብርቱ ጉዳይ ስለሆነ ለፖለቲከኞች የሚተው አይደለም ወደሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ፡፡
ቻርልስ ደጎል
በእኛ ዘመን ከፖለቲካ መራቅ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁሉም ጉዳዮች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ጆርጅ አርዌል
ፖለቲካ ፍልስፍናን በተካበት ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡
ጆሲ ማርያዲ ኢካዲ ኪውይሮዝ
ፖለቲከኛ፤ ጌታ ለመሆን አገልጋይ መስሎ ይቀርባል፡፡
ቻርልስ ደጎል
እውነት በአብላጫ ድምፅ አይወሰንም፡፡
ዶግ ግዊን
ለችግሮቻቸው የቀድሞውን አስተዳደር ያልወቀሱ ብቸኛ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሺንግተን ናቸው፡፡
ያልታወቀ ፀሐፊ
ወግ አጥባቂ ማለት ምንም ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ መሰራት የለበትም ብሎ የሚያምን ሰው ነው፡፡
አልፍሬድ ኢ.ዊጋም
የከተማዋን መክፈቻ ቁልፎች ለፖለቲከኛ ከመስጠት ይልቅ መቆለፊያዎቹን መቀየር ሳይሻል አይቀርም፡፡
ዶውግ ላርሰን
እጅግ በጣም ጥቂት ሴት ፖለቲከኞች ያሉበት ምክንያት ሁለት ፊት ላይ ሜክአፕ መቀባት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡
ማዩሪን መርፊ
የቤተሰብ ሐረግህን ለማስጠናት ለምን ገንዘብ ትከፍላለህ፤ ፖለቲካ ውስጥ ግባና ተቀናቃኞችህ ያጠኑልሃል፡፡
ያልታወቀ ፀሃፊ
አንድ አሜሪካዊ ለዲሞክራሲ ለመዋጋት ውቅያኖስ ይሻገራል፤ ለብሄራዊ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ግን ጎዳና አይሻገርም፡፡
ቢል ቫውግሃን
ድምፅ መስጠት (ምርጫው) አይደለም ዲሞክራሲ የሚባለው፤ የድምፅ ቆጠራው ነው፡፡
ቶም ስቶፓርድ

Published in ማራኪ አንቀፅ

               አንድ የቅርብ የምለው ጓደኛዬ በሰርጉ እለት እንድገኝለት የጋበዘኝ ከሁለት ወር በፊት ነበር፡፡
እኔም ጥሪውን አክብሬ ደስታውን ለመካፈል ከመለስተኛዋ የሠርግ አዳራሽ ውስጥ ተገኘሁ፡፡ ለስለስ ባሉ የሠርግ ዘፈኖች ምሣ ከተበላ በኋላ የመጠጡ፣ ዘፈኑ እና የታዳሚው ስሜት እየጋለ መጣ፡፡ አንድ ቁርጥ እንጀራ ለማንሳት የተጀነነ ትከሻ ሁሉ በጠጁ ብርታት የቅምጥ እስክስታውን ያስነካው ጀምሯል፡፡ ፀጋዬ እሸቱ “ተይሙና ተይሙና” ሲል ሠርገኛውም “አሆሆይ ሙና” እያለ ያጅበዋል፡፡ መቼም የሐበሻ ባህሪ ሀዘንና ደስታን እስከጫፉ እንዲለካ ሆኖ ነው የተፈጠረው፡፡ የሐበሻ ዘፈንም እንደዛው ከሙሾ እስከ ጭፈራ፡፡ ዲጄው በተቀመጠበት ጭፈራ የነሸጠውን ታዳሚ በመመልከት፣ አከታትሎ የባህል ዘፈኖቹን መልቀቅ ጀመረ፡፡ አሸብር በላይ፡- “ለበላይ ቤልጅጉ ለዓባይ ጣና አለለት ለእኔም እሷን ሰጠኝ፣ ጎጃም ዘር ይውጣለት”
በዚህ ግዜ ሙሽራው ጓደኛዬን ጨምሮ ግማሽ የአዳራሹ ሰው ተነስቶ፣ በእስክስታ መርገፍገፍ ጀመረ፡፡ የሚገርመው ነገር ከላይ በሀገር ጀግንነቱ የሚታወቀውን በላይ ዘለቀን አርዓያ አድርጎ የጀመረው ዘፋኝ፤ ለአንዲት ሴት ጠብ-መንጃ ይዞ ሐገር አይብቃኝ ማለቱ ሳያሳፍረው “ጎበዝ ከሠነፉ ፈረስ ከእግረኛ
    እኔ ነኝ ያለ ይሞክረኛ”
እያለ የኔ ያላት ጉብል ላይ ያጎበጎበውን በጥይት እሩምታ ተራራ ለተራራ ሲያዳፋው ክሊፑ በአይኔ መጣ፡፡
ሙሽራው ጓደኛዬ እራሱ አጨፋፈሩ ሙሽሪትን በፍቅር መፈቃቀድ ሳይሆን ነፍጥ አንግቦ በዙሪያዋ ያንዣበበውን ሁሉ… ሠላም የሚላትን ሳይቀር በጥይት እሩምታ አስፈራርቶ ያገባት ነው የሚመስለው፡፡ እኔ የምለው ህግ ባለበት ሐገር፣ ሠው በሠላም ወጥቶ በሠላም ሊገባ በሚገባበት ሃገር፣ ህገ-መንግስቱን ንዶ ህገ-እንስቱን ሊጠብቅ እሳት ጎራሽ ብረት ታጥቆ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል ዘፋኝ ሀይ ባይ አጥቶ፣ “ኢ-ቲቪን” ጨምሮ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያውን ሲያጨናንቅ አይገርምም? እውነትም አሸብር! ጥበብስ የህብረተሠቡን ጎጂ ማህበራዊ እሳቤን በሀይሏ መግራት ሲገባት፣ የእብሪተኞች አርማ መሆኗ አያሳዝንም? ይሄ ሲገርመኝ የዚህ ዘፈን መንታ ወንድም የሚመስሉ የባህል ቸብቸቦዎች የታዳሚውን የጭፈራ  እልህ ማስወጣት ጀመሩ፡፡ ሠማኸኝ በለው ቀጠለ፡- “በለው!” የዚህንም ዘፈን ምስል በቴሌቪዥን መመልከቴ ታወሰኝ፡፡ ህግ አላከበርክም ተብሎ ሁለት አመት በእስር ካሳለፈ በኋላ ሠሜ አንድ መቀመጫዋን “ኧረ ምኑን ሠጠሽ” እያለ የሚያደንቅላትን ኮረዳ የተመኘበትን ሠው ካልገደልኩ እያለ የሚፎክርበት ዘፈን ነው፡፡ በዚህ ማን ይነካኛል ብሎ ነው መሠለኝ፡-
“ምን ፈልጎ አጅሎት የሚመላለሰው
በክትክታ ሽመል ግንባሩን ልግመሰው………ጭንጋፍ ነው ጭንጋፍ ነው ጭንጋፍ ነው ሙትቻ
ተውልኝ ብያለሁ ቆይ ብቻ ቆይ ብቻ…….”
እግዜር ያሳያችሁ እንግዲህ ይሄ ሠው “ማር ዘነብ” የሚላትን ጉብል ተሳስቶ የነካበት እንደሁ ወይ መንካት! ኧረ ቀና ብሎ ያየበት እንደሆን “ጭንጋፍና ሙትቻ” ተብሎ ሞራላዊ ባልሆነ መንገድ የተሠደበው አፍቃሪ፤ ግንባሩ የክትክታ ሲሳይ መሆኑ ነው፡፡
   ስለዚህ ያሻውን የመውደድ ሠብዓዊ መብት ያለው አፍቃሪ ጉልበተኛን ፈርቶ ዝም ነዋ! ማን ከእብሪተኛ ጋር ይጋፋል፡፡ ጀግና ነኝ ካለ ደግሞ ወይ ብትርን በብትር ወይ ብትርን በጥይት ሊመክት ይነሳል፡፡ ከዚያ ደም ወደ መፋሠስ፡፡ ኢ-ቲቪም ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ እኚህን አነስተኛ ጦርነቶች እያስተላለፈልን ይገኛል፡፡ በምስል ይስሩ አይስሩ ያላረጋገጥኳቸው፣ በየራዲዮ ጣቢያዎቻችን “ለክቡራን አድማጮቻችን” እየተባለ በግብዣ መልክ ከሚበረክቱልን መሠል ዘፈኖች የታወሱኝን ላስከትል፡- ይሆኔ በላይ /ይሁን የበላይ/ “ገላጋይ”ን እንይ፡-
“ቆይማ ቆይማ ላሳየው ቆይማ
አንቺን ብሎ መጥቷል ነገር የተጠማ
ደሞ ለወንድነት ድሮም ካልታማ
ባንቺ ይፈትኑኝ ይታይ የኔ ግርማ”
ይህም ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው እብሪት የተሞላባቸው ዘፈኖች መንትያ
ነው፡፡ አዝማቹ ላይ እንደሚታየው የአማርኛ ፍቺ ከሆነ፤
ማፍቀር፡- ነገር መጠማት ነገረኝነት
ጀግና፡- አፍቃሪን ድባቅ የመታ /የወደዳትን የተመኘበትን/ ሆኖ ቀርቧል፡፡ የጡንቻ
   መለኪያው የመስዋእትነት ጥግ ለሴት መሞት! ለሴት መግደል! በሆነበት ጥበብ ለሀገር የወደቁ ለሀገር የተሠው አርበኞቻችንን ምን ስም ልናወጣላቸው ይሆን? ይሁኔ ይቀጥላል፡-
“… ቢሻው በማባበል ቢሻው በሽመሉ
   ይመለስ የለም ወይ ሁሉም እንዳመሉ
እንደምናውቅበት በፍቅር ማስከርን
የት እናጣዋለን ጥሎ መፎከርን፡፡”
የመጀመሪያዎቹ ሁለት ስንኞች ሀሳብ ልክ እንደ ውሻ
ሠው የሠጠውን መብት ተቀብሎ የሚኖር ሠው ካልሆነ በቀር፣ ሠብዓዊ መብቴን ተጠቅሜ
ልውደድ፣ ላፍቅር ለሚል ሰው ዘፋኙ ምንም ርህራሄ እንደሌለው፣ በቀጣዮቹ ሁለት ስንኞች
ደግሞ እንደድሮ አንበሳና  ነብር ገድሎ እንኳን መፎከር ወንጀል በሆነበት ዘመን፣ እንኳን
የሠው የእንስሳት መብት ተሟጋቾች በተፈጠሩበት ጊዜ፣ ክቡሩን የሰው ልጅ አንፈራፍሮ
መሬት ጥሎ ጀግና ነኝ ብሎ መፎከር፣ እሰይ አበጀህ የሚያስብል ጀብድ ሆኖ ቀርቧል፡፡
የቀጣዮቹ ስንኞች አንድምታም ከእ አይሻል ዶማ ነው፡፡ ይሄ‘ኮ ሠልጠነናል የምንልበት ዘመን
ነው ጃል፡ ዛፍን ያለ አግባብ መቁረጥ ደሞ ወንጀል እስከመሆን የደረሠበት ጊዜ ላይ ሆነን
እንኳን ለዛፍ ለሠው ግድ የሌለው ዘፋኝ፡-
“ባንድ ድር ይበቅላል በትርና አበባ
በልምምጥ ባይሆን ለምጠኸው ግባ” ይልሃል፡፡
እንግዲህ ያቺን ጉብል ጥሎብህ የወደድክ ሆይ፤ ከዱሩ የፈካ አበባ ቀጥፌ ላበርክትላት ብለህ እንዳታስብ፤ ምክንያቱም አጅሬ ካንተ ቀድሞ ከጫካው በትሩን ቆርጦ መልምሎ፣ ላናትህ ሲሳይ የሚሆን ገፀበረከት ሊያበረክትልህ ተዘጋጅቷልና፡፡ እዚህ ላይ ከነዚህ ዘፈኖች መልእክት ጋር ተያይዞ መነሳት የሚገባው ጉዳይ ደሞ ሴቶች ፍቅር ላይ ያላቸው ተሳትፎ ነው፡፡ ግጥሞቹ ላይ እንደምንመለከተው አንዲት ሴት እንደ ሪሲሊንግ ቀበቶ ፍልሚያውን ለሚያሸንፈው ጡንቸኛ በሽልማት መልክ የምትበረከት ስጦታ እንጂ ቀልቧ የተመኘውን፣
የሕይወቴ መንገድ የምትለውን ሠው የመምረጥ መብት የሌላት ሆና ትታያለች፡፡ ምናልባት እኮ ያቺ ሴት በፍቅር ልቧ የቀለጠለትና ነብሷም የመነነለት ያ በፍልሚያው ተሸንፎ የወደቀው ወጣት ይሆናል፤ ወድቆ ሲፎከርበት ሕይወቱ ቢያልፍ እንኳን ፍቅሯ ከሱ ጋር ተያይዞ መቃብር መውረዱ እኮ ነው፡፡ ከዚያም ከገዳይም ጋር አብራ ልትኖር! አይበለውና ይህ ቢፈጠር፣ ልቧ በፍቅር እጦት የጠለሸባት ሴት እንዲህ የምትል አይመስላችሁም?
“ብትር የለም እንጂ ለሴት የሚቆረጥ
ጀግና የለም እንጂ ከሴት የሚፋለጥ
በክትክታ…. አልቄ
ከመሬት….. ወድቄ
ካንተ ጋር መሞትን ነበር ልቤ ሚመርጥ”
የሷ ይብቃንና የዘፈኑን ማሳረጊያ ግጥም እንይ፡፡
“ወዲህ ወዲያ የለም ቀና ነው ነገሬ፤ ቀልድ መች አውቃለሁ ባንቺና ባገሬ” እኔም እንዲ አልኩ፡- ሀገር ማለት ወንድም፣ ሀገር ማለት እህት፣ ሀገር ማለት ጎረቤት፣ የመንደሩ ሠው፣ ብቻ ሀገር ማለት ሁሉም ሠው ነው፤ ከሁሉም ነገር ሠውና ሠውነት ይቀድማል፡፡ አገር ማለት የሠው ደም የጠጣ መሬት አይደለም! በፍቅር የፀና፣ በሞራላዊ ህግ የተገዛ ማህበረሠብና በሠላም የተሳሠረ ማንነትን በአንድ የሚያኖር ምድር ነው፤ ሀገር ሀገር የሚሸተው፡፡ የራስ ጠላት ከራስ ወገን አበጅቶ፣ በዓመፅ ክንድና ቂም በቀል ቢተላለቁ ለየትኛዋ ሀገር ነው የትኛውን የውጪ ጠላት የሚመክቱላት?! አንድ የመጨረሻ ዘፈን ልመርቅና
ትዝብቴን ላሳርግ፡፡
“የኔአለም አንቺን ያለውን
በሳንጃ ሆዱን…”
የዚህኛው ደሞ ይብሳል፡፡ ከግድያ ወንጀሎች ሁሉ ሠውን በስለት መግደል በአሠቃቂነቱ የሚስተካከለው ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ዘፈን ላይ ግን የፍቅር መግለጫ ሆኖ ቀርቧል፡፡ /አያስቅም?/ ሚዲያዎቻችን ግን መሠል ሙዚቃዎችን ለማስተላለፍ ምንም አያግዳቸውም፡፡ “ሼም” የለም እንዴ? ከዚህ አንፃር እኮ ፖሊስና ህብረተሰብ ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡ የዝርፊያ፣ የድብድብና የጥይት ግድያዎች ሚዛናቸው ይቀላል፡፡ ቲቪያችን ግን በመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ሳይቀር ለመልቀቅ እፍረት የለውም፡፡ እንዲህ አይነት ሙዚቃዎች  ለመዝናኛ የሚሆኑ ከሆነ ፖሊስ ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡ ወንጀሎችንም እሁድ መዝናኛ ላይ ያቅርብልን፡፡ ሕዝቤም እየተነሳ ይጨፍርባቸው፡፡ በርግጥ እንዲህ አይነት እብሪት የተሞላባቸው ዘፈኖች ዛሬ ላይ አይደለም መሠራት የጀመሩት፡፡ ከድሮ ጀምሮ ሙዚቀኞቹ ከበቀሉበት ማህበራዊ እሳቤ እየተነሱ ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን ጥያቄው እንደ ጥበብ ምንድነው ማድረግ ያለብን ነው፡፡ የሕብረተሰቡ ማህበራዊ የአኗኗር ዘይቤና ፍልስፍና ቢሆን እንኳን ይሄን ጎጂ ባህል ማራቅ ነው እንጂ እውቅና መስጠትና ማባባስ ነው ወይ የጥበብ ድርሻዋ? እዚህ ላይ የመስፍን በቀለን “ደመላሽ” ማንሳትና ማመስገን ይገባል፡፡ ልማድ ወጥሮት ደም መቃባትን እንደ አንድ የኑሮ አካል የያዘን ማህበረሠብ፣ የፍቅርን ጉልበትና ኃያልነት ልማዱን ገድሎ ያሳየን ሙዚቃ ነው፡፡ እንዲህ ነው ጥበብ ማህበረሠብን አንድ እርምጃ ስትቀድም፣ ጥበብ በቂም ሀረግ የተተበተበውን የደም ጥም በፍቅር ስላቷ ስትበጥስ፡፡ የአንድ ሰው ግላዊ የስነልቦና እሳቤ በመኖሩ ላይ ከመንፀባረቅ አልፎ ወደ ቤተሠብ፣ ጎረቤት እያለ ወይ ማህበራዊ እሳቤ ያድጋል፤ ይህ ከሌሎች ጋር ሲጠራቀም ደግሞ ያንዱን ማህበረሠብ የኑሮ ዘይቤ ይሠራል፡፡ ይህ ማለት ያንድ ሠው ቀናም ሆነ እኩይ አስተሳሰብ ለማህበረሠቡ ግብአት ነው ማለት ነው፡፡ እኛ በራሳችን እንደግለሠብ እንኳን ቀናና አስተማሪ ስራ ሰራን ማለት ቢያንስ አንድ ጉድፍ እንዳጠራን ይቆጠራል፡፡ ይህ በብዙዎች ዘንድ እያደገ ሲመጣ ደግሞ ለውጥ ይሆናል፡፡ ይህን ማድረግ ባንችል እንኳን ዝምታን መርጠን መቀመጥና ለጎጂው ማህበራዊ እሳቤ አንድ ድጋፍ መቀነስ አለብን፡፡ ስለዚህ እባካችሁ እናንት ትምክህተኛ የባህል ዘፋኞቻችንና ገጣሚዎቻቸው፤ ጥበባችሁ ፈቅዶ ባታስተምሩን እንኳን እሳት አትለኩሱብን፡፡ ዝም በሉን፡፡

Published in ጥበብ

        በሰባት የዓለም ሀገራት 7,540 ያህል ሆቴሎችን የሚያስተዳድረው ዋይንድሃም ሆቴል ግሩፕስ፤ “ራማዳ አዲስ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ሆቴል ከአንድ ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ ሥራ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ይገነባል የተባለው ይኸው ሆቴል፤ 128 የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎችና 8 የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ክፍሎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡
ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው የአለማቀፍ ሆቴሎች ስብሰባ ላይ የተሳተፈው ዋይንድሃም ሆቴል ግሩፕስ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ ሆቴሉ በ2008 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብሏል፡፡
የ“ራማዳ አዲስ” ሆቴል ባለቤት አቶ አዱኛ በቀለ፤ ኩባንያቸው ኤዲኤም ቢዝነስ ፒኤልሲ በአለማቀፍ ደረጃ የገነነ ስምና ዝና ካለው ዋይንድሃም ሆቴል ግሩፕስ ጋር በጋራ በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሆቴሉ ሲጠናቀቅ የሃገሪቱን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ወደ ፊትበማራመድ ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባሻገር ለ250 ያህል ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ “ራማዳ” በሚለው ስም በአለማቀፍ ደረጃ 830 ያህል መካከለኛና ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች እንዳሉ የተጠቆመ ሲሆን በዚህ አመት የብራንዱ 60ኛ አመት ይከበራል ተብሏል፡፡
 የዋይንድሃም ሆቴል ግሩፕስ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኘው በአሜሪካ ኒው ጀርሲ ሲሆን በ71 የዓለም ሃገራት 650,200 ክፍሎች ያላቸው 7540 ሆቴሎችን ያስተዳድራል፡፡
የሆቴል ግሩፑ በአፍሪካ ውስጥ በጋና፣ በሞሮኮ፣ ናይጄሪያና ቱኒዚያ ዋይንድሃም በሚለው ስም ሆቴሎች ያሉት ሲሆን በኬንያ፣ ታንዛኒያና ናይጄሪያ ደግሞ ራማዳ በሚል 6 ሆቴሎችን ከፍቷል፡፡
 በኢትዮጵያ የሚከፈተው “ራማዳ አዲስ” ሆቴል 7ኛው ይሆናል ተብሏል፡፡ ሰሞኑን በሸራተን አዲስ በተከናወነ ስነስርአት ላይ ዋይንድሃም ሆቴል ግሩፕ “ራማዳ አዲስ”ን ለማስተዳደር ከኤዲኤም ቢዝነስ ጋር የማኔጅመንት ኮንትራት ውል ተፈራርሟል፡፡

Page 12 of 15