ከ350 ሺ በላይ ተመዝጋቢዎች ይጠበቃሉ
ምዝገባው የሚካሄደው የስራ አጡን ቁጥር ለማወቅ ነው ተብሏል

        በአዲስ አበባ  ቤት ለቤት የሚካሄደው የስራ አጦች ምዝገባ አላማ በከተማዋ ያለውን የስራ አጥ ቁጥር ለማወቅ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ከ350 ሺ በላይ ተመዝጋቢዎች ይጠበቃሉ ተብሏል፡፡ ወደ 9 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት ተይዞለት ከመስከረም 8 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የስራ አጥነት ምዝገባ፤ በዋናነት በከተማዋ ምን ያህል ስራ አጥ አለ የሚለውን ለማወቅና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ፣ የስራ እድሎችን ለማመቻቸት የታቀደ ፕሮጀክት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የኢንዱስትሪ ሰላምና የሙያ ደህንነት ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ካሳ ስዩም ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ እንዲህ መሰሉ ምዝገባ ከዚህ ቀደምም በየጊዜው በከተማዋ እንደሚካሄድ አስታውሰው፣ የአለማቀፍ ሰራተኞች ድርጅት (ILO) ለአገራት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፣ በከተማዋ ያለውን የስራ አጥነት ሁኔታ በተጠናከረ መረጃ የማደራጀት፣ የመተንተንና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተንተርሶ መፍትሄ የመስጠት አካል ነው ብለዋል፡፡ የስራ አጥነትን ሁኔታ አጥንቶ የስራ እድሎችን ማመቻቸት የሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮው አንዱ ኃላፊነት እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ምዝገባው ከወር በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደታቀደ ጠቁመዋል፡፡ ቤት ለቤት እየተካሄደ ያለው የስራ አጥነት ምዝገባ፣ ተመዝጋቢዎች በምን አይነት የስራ መስክ ላይ ቢሰማሩ ይመርጣሉ የሚለውን ያካተተ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ካሳ፤ ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ የተሰበሰበው መረጃ ተተንትኖ፣ ተመዝጋቢዎች በሚፈልጉት የስራ መስክ ስልጠና ወስደው የሚሰማሩበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል፡፡
ቢሮው ስራና ሰራተኛን በነፃ የማገናኘት ኃላፊነቱን ለመወጣትም ራሱ ስራ አጦችንና ስራን ከማገናኘት ባለፈ ፍቃድ የተሰጣቸው ስራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ስራ አጦችን ስራ በማስያዝ ተግባር እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ምዝገባው ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ለየት የሚያደርገው ጥናትን መሰረት አድርጎ የተለያዩ ማመላከቻዎችን መጠቀሙ እንደሆነ የገለፁት አቶ ካሣ፤ በከተማዋ ያሉ ስራ አጦች በየትኛው የስራ መስክ ነው የበለጠ መሰማራት የሚፈልጉት የሚለውን ለይቶ ለማወቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ መረጃውን በመጠቀምም የተለያዩ የመንግስት እና የግል የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የስልጠና መስካቸውን እንዲፈትሹ አጋዥ ይሆናል ሲሉ ኃላፊው አክለው ገልፀዋል፡፡
በምዝገባው ወቅት እድሜና የትምህርት ደረጃ የመሳሰሉትን ጨምሮ በትክክልም በአዲስ አበባ ነዋሪ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይሰበሰባሉ ተብሏል፡፡ በአለማቀፍ የሰራተኞች ድርጅት መስፈርት መሰረት እድሜያቸው ከ14-18 ዓመት ያሉት በወጣት ስራ ፈላጊነት ይመዘገባሉ ያሉት ኃላፊው፤ በዚህ የእድሜ ክልል ላሉ በአቅማቸው ሊሰሩት የሚችሉት ስራ ይዘጋጅላቸዋል ብለዋል፡፡ አክለውም እድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ በዚህ የምዝገባ ሂደት አይካተቱም ብለዋል - ኃላፊው፡፡ በየዓመቱ በርካታ የከተማዋ ስራ አጦች የስራ እድል እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ካሣ፤ በ2006 ዓ.ም ከ230 ሺህ በላይ ለሆኑ ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ በዚህ የስራ አጦች ምዝገባ ፕሮጀክትም ከ350 ሺህ ያላነሱ ሰዎች ይመዘገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ምዝገባው የቤት ሰራተኞችን ጨምሮ ማንኛውም ተቀጥሮ የሚሰራና ገቢ የሚያገኝ ግለሰብን አይመለከትም ተብሏል፡፡
ስራ አጦችን ለመመዝገብ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ እንደተገባ የተናገሩት ኃላፊው፤ 734 ሰራተኞች በኮንትራት ተቀጥረው በከፍተኛ አማካሪነት፣ በሱፐርቫይዘርነት፣ በአስተባባሪነት እና በመረጃ አሰባሰቢነት እየተሳተፉ ነው ብለዋል፡፡ መረጃ ሰብሳቢዎችም በዲግሪ የተመረቁ እንደሆኑ አክለው ገልፀዋል፡፡
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሁሉም የክልል ከተሞች በ2007 ዓ.ም በሃገሪቱ ምን ያህል ስራ አጦች አሉ የሚለውን በዘመናዊ መንገድ ለይቶ ለማወቅ ተመሳሳይ ምዝገባ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ከዚህም ቀደም በሃገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ምን ያህል ስራ አጦች እንዳሉ አመላካች የሆነ በጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ መረጃ እንዳልነበረ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡  

            መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በማዕከሉ ባዘጋጀው የመስቀል በአል አከባበር ስነስርአት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገች፡፡ በእለቱ የተገኙት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ልዩ ረዳት አቶ አሰፋ መብራቴ፤ ከማዕከሉ ጋር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍቃደኝነት ገልፀዋል፡፡ በመስቀል አከባበር ስነስርአት ላይ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የመንግስት አካላት የተገኙ ሲሆን ዝግጅቱን በንግግር የጀመሩት የመቄዶንያ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ብርሀኔ ጸጋዬ እና የድርጅቱ መስራችን ስራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ ማዕከሉ በአራት ማዕከላት 650 በላይ ለሚሆኑ ተረጂ ወገኖች ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልፀው ከመንግስት የጠየቀውን 30.000 ካሬ ሜትር ቦታ እንደተሰጠው፣ በቀጣይ አምስት አመታት ውስጥ የተረጂውን ቁጥር ወደ 10,000 /አስር ሺህ/ ለማሳደግ ዝግጅት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
ማዕከሉም የጎበኙትና 100.000 ብር የለገሱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን ፓትሪያርክ ብፁህ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብጹሃን ጳጳስ፣ ይህንን እርዳታ እንዲያደርጉ የረዳቸውን እግዚአብሔርን አመስግነው ማዕከሉ እያከናወነ ያለው ተግባር እግዚአብሔር የሚወደው መሆኑን የገለፁ ሲሆን እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ወደፊት በማስተባበርም ሆነ በገንዘብ እግዚአብሔር በሰጠን፣ አቅማችን በፈቀደ እንቀጥልበታለን ብለዋል፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ልዩ ረዳት አቶ አሰፋ መብራቴ፤ ይህ ተቋም ከሌሎች የተለየ እውቅናና ክብር እንድንሰጠው ያደረጉ ተግባሮችን እየሰራ ያለ ማዕከል ነው፡፡ ከማዕከሉ ጋር አብረን ለመስራት ፈቃደኛ መሆናችንን ማረጋገጥ እንወዳለን ያሉ ሲሆን፤ የወረዳ 9 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ በፈቃዱ በበኩላቸው፤ የሀገር ባለውለታ ለሆኑት አረጋውያን እየተደረገ ያለውን ድጋፍና እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እናደንቀዋለን፤ ከዚህም ባሻገር እንደ አስተዳደር ልንተጋገዝ የሚገባ ጉዳይ ሲገኝ ተጋግዘን ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

               በሩትገርስ ዩኒቨርሲቲና በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ ጥናት፤ በትዳር ህይወት ውስጥ ከባልየው ይልቅ የሚስትየው ደስታ ለግንኙነታቸው ህልውና የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ ተረጋገጠ፡፡ ተመራማሪዎቹ በአማካይ ለ39 ዓመታት በትዳር የዘለቁ ጥንዶች ላይ ጥናት እንዳደረጉ ታውቋል፡፡ ጥንዶቹ የትዳር አጋሮቻቸው ያደንቋቸው፣ ይሞግቷቸው ወይም ያበሽቋቸው እንደሆነ የተጠየቁ ሲሆን በ24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ በሚያከናውኗቸው የተወሰኑ ተግባራት - ለምሳሌ አስቤዛ መሸመት ወይም ቴሌቪዥን መመልከት … ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ተጠይቀዋል፡፡ አብዛኞቹ የጥናቱ ተሳታፊዎችም በትዳር ህይወታቸው ከፍተኛ እርካታ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡ ሴቲቱ በባሏ ደስተኛ ከሆነች እሱም በአጠቃላይ ህይወቱ የበለጠ ደስተኛ ይሆናል - ስለትዳሩ የሚሰማው ስሜት ምንም ይሁን ምንም፤ ብሏል ጥናቱ፡፡
ከጥናት ፀሃፊዎቹ አንዷ የሆኑት ዲቦራህ ካር ለሩትገርስ እንደተናገሩት፤ “ሚስቲቱ በትዳሯ ስትረካ፣ ለባሏ የማታደርገው ነገር የለም፤ ይሄ ደግሞ በህይወቱ ላይ በጎ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ወንዶች ስለትዳር ግንኙነታቸው ብዙም አያወሩም፤ ስለዚህም በትዳር ህይወታቸው ደስተኛ አለመሆናቸው ወደሚስቶቻቸው ላይጋባ ይችላል”
ሰውየው በትዳሩ ደስተኛ ካልሆነ፣ ሚስቱ ህይወቱን ብሩህ ለማድረግ የምታከናውናቸው ትናንሽ ነገሮች የደስታ እጦቱን ሊሸፍነው ይችላል፡፡ ወንዶች የጥናቱ ተሳታፊዎች ከሚስቶቻቸው ይልቅ ትዳራቸው መልካም ነው ብለው የሚያምኑ ሲሆን ትዳራቸው ከፍ ያለ ደረጃ ላይ እንደሆነ የሚያስቡ ተሳታፊዎች በሙሉ ግን በአብዛኛው የህይወት እርካታን የተጎናፀፉ ሆነው ተገኝተዋል - ያለምንም የፆታ ልዩነት፡፡

ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው ያገኙት ሌላ ነገር ደግሞ ባሎች ሲታመሙ የሚስቶቻቸው ደስታ መጨመሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ለባሎቻቸው እንክብካቤ የሚያደርጉት እነሱ በመሆናቸው ነው ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ሚስቶች ሲታመሙ ብዙ ጊዜ ለእርዳታ ፊታቸውን የሚያዞሩት ወደ ሴት ልጆቻቸው ነው፡፡ እናም የባሎች የደስታ መጠን ሳይለወጥ ባለበት ይቆያል፡፡ የትዳር ህይወት የጥራት ሁኔታና የደስታ መጠን ሰዎች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ በጤናቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በዴቦራህ የጥናት ፅሁፍ  መሰረት፤ “ጥራት ያለው ትዳር አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በኋላ ዘመን ውጥረት ፈጣሪ ከሆኑ ጤና የሚያላሽቁ ተፅዕኖዎች መከላከያ ጋሻ ያጎናፅፋል፤ እንዲሁም ጥንዶች ጤናና ህክምናን የተመለከቱ አስቸጋሪ ውሳኔዎችን በቅጡ ለመወሰን ያግዛቸዋል፡፡”
በእናንተ የትዳር ግንኙነት በጥናቱ የተመለከተው ዓይነት ውጤት ገጥሟችኋል? ቢያንስ በግል ካስተዋልኩት፤ በትዳር ግንኙነታቸው ደስተኛ የሆኑ ሴቶች ለትዳር አጋሮቻቸው ተጨማሪ በጎ ነገር ለማድረግ ከመንገዳቸው እንደሚወጡ ተገንዝቤአለሁ፡፡ ይሄ ማለት ግን ወንዶች እንዲህ መሰሉን ነገር አያደርጉም ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ ጥናት የምንረዳው አንድ ዋና ቁም ነገር፣ ሚስት ደስተኛ ስትሆን የትዳር ህይወት የሰመረ እንደሚሆን ነው፡፡ ንግስቲቷ ደስተኛ ስትሆን፣ መላው ቤተሰብ ደስተኛ ይሆናል እንደማለት!!

Published in ባህል

በገጣሚ እርቅይሁን በላይነህ የተፃፈው “እርቃንሽን ቅሪ” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ በመፅሃፉ ጀርባ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት፤ በመድበሉ የተካተቱት ግጥሞች ጠንካራ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት መምህር የሆኑት ጋዜጠኛ አስተዋይ መለስ በበኩላቸው፤ “ታሪክን የሚያወሱ ጥሩ ግጥሞች ናቸው” ሲሉ አድንቀዋል፡፡ በ132 ገፆች 77 ግጥሞችን ያካተተው መፅሀፉ፤ በ25 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡
ገጣሚው ከዚህ ቀደም “ያልተጠቡ ጡቶችን” የተሰኘ የአጫጭር ልብወለድ መድበልና  “የኢትዮጵያ ታሪክ ከኢማም አህመድ እስከ አጼ ቴዎድሮስ” የሚል የታሪክ መፅሃፍ ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል፡፡

Monday, 06 October 2014 08:16

ጋብቻ እና ትራጀዲ

          አዲሱን ትውልድ ግለፀው ብባል መጀመሪያ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው ቃል “ኮንዶሚኒየም” የሚል ነው፡፡ በኮንዶሚኒየም ያልኖረ፣ በኮንዶም ያልተጠቀመ የአዲሱ ትውልድ አባል አይደለም፡፡ ግን “አያዎ” በኮንዶሚኒየም እና በኮንዶሙ መሀልም ይፈጠራል… በኮንዶም ይጠቀሙ የነበሩ ፍቅረኛሞች፣ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ገብተው መኖር ሲጀምሩ በኮንዶም መጠቀሙን ያቆሙታል፤ በገቡ በጥቂት ወራት ሴቶቹ ያረግዛሉ፡፡
እኔ ከመሬት ቤት ወደ “ሰቀላ ቤት” የመውጣቱ እድል ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠመኝ ኮንዶሚኒየም ቤት የተከራየሁ እለት ነበር፡፡ ኮንዶሚኒየም ቤት የመግዛት አቅም ያላቸውም አሉ፡፡ እኔ ግን አቅሜ በመከራየት የተወሰነ ነው፡፡ የመከራየቱም እድል የገጠመኝ ሰሚት የሚባለው ሰፈር፣ መቶ ሀምሳ ሺ አባወራዎችን ለማቆር የሚችል ኮንዶሚኒየም ተገንብቶ ካለቀ በኋላ ነበር፡፡
እኔም እንደ ሌሎቹ ወጣቶች ፍቅረኛዬን አንጠልጥዬ ወደ ሰሚት ተሰደድኩ፡፡ አሁን ሁለት ወር ገደማ ሆኖኛል፡፡ የምኖረው አራዳ ተብሎ ከሚጠራው የሰሚት ኮንዶሚኒየም ቀበሌ ነው፡፡ የራሴ መብራት እና የውሃ ቆጣሪ አለኝ፡፡ የራሴ በር እና የራሴ ሽንት ቤት፣ የራሴ ወጥ ቤት አግኝቻለሁ፡፡ አንዱ ፎቅ አንድ መንደር ማለት ነው፡፡ የመንደሬን ሰዎች መንገድ ላይ ባገኛቸው አላውቃቸውም፡፡ የምንተዋወቀው ደረጃ ላይ ስንወጣ ወይንም ስንወርድ የተገናኘን እንደሆንን ብቻ ነው፡፡ ያኔ ሰላምታ እንለዋወጣለን፡፡
ገና ሶስት ወር ስላልሞላኝ ማን ምን እንደሆነ ወይንም ከየት እንደመጣ የማወቅ ደረጃ ላይ አልደረስኩም፡፡ የማውቀው ነገር እያንዳንዱ ተከራይ እቃውን ጭኖ የሚመጣው በ“አይሱዙ” እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ “አይሱዙ” መኪና መጫን ከሚችለው አቅም በላይ ንብረት ያፈራ አባ ወራ፣ ለኮንዶሚኒየም አይመጥንም፡፡ የቪላ ቤት እቃ ይዞ ኮንዶሚኒየም መግባት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ሽማግሌዎች በብዛት አይገኙም፡፡ ሽማግሌ በህይወት ልምድ የሚዳብረውን ያህል ንብረትም መሰብሰቡ  አይቀርም፡፡ እናም የኮንዶሚኒየም ህይወት ቢፈልገውም ይቀርበታል፡፡
ወጣቶች ብቻ ይከራያሉ፡፡ በአይሱዙ ይዘው የሚወጡት እቃ ጠርቀም አለ ከተባለ ሶፋ፣ ቁምሳጥን፣ ምንጣፍ፣ ፍሪጅ፣ አልጋ፣ ፍራሽ፣ ዲሽ/ቲቪ፣ እና መጋረጃ ይጠቀልላል፡፡ አነሰ ከተባለ ፍራሽ እና ልብስ ብቻ ይሆናል፡፡ ብቻቸውን የተከራዩ ወንዶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሴት ይዘው መምጣት ይጀምራሉ፡፡ ጀምረው ከአንድ ሴት ጋር ይቀጥላሉ ወይንም ይለዋውጣሉ… ግን በምንም አይነት ብቻቸውን አይሆኑም፡፡ ሴቶቹ በአብዛኛው ብቻቸውን አይከራዩም፤ ከተከራዩም ወንድ ራሱ በር አንኳኩቶ ይመጣላቸዋል፡፡ ጥሩ ምግብ አብስለው ሽታውን በመስኮት መልቀቅ ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው… ወንድ ‹ከተፍ› ይላል፡፡ ምግብ ማብሰል የማይችሉ፣ ሱቁ አካባቢ አንድ ሁለት ጊዜ መዘዋወር ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ በፎቆቹ ግድግዳዎች ላይ “ለትዳር ፈላጊዎች” በሚል ግልፅ ማስታወቂያ ለወንድም ሴት፣ ለሴትም ወንድ የሚያቀርቡ አይጠፉም፡፡ ሰራተኛ ቀጥሮ ደመወዝ ከመክፈል ሰራተኛዋን አቅፎ ሚስት ማድረግ የተሻለ ነው ብለው የጨከኑም አሉ ይባላል፡፡
በአጭሩ ግን ኮንዶሚኒየም አነስተኛ እና ጥቃቅን ባል እና ሚስቶች ማቆሪያ፣ ማግባቢያ እና ወጣቱን ትውልድ አይኑን በአይኑ እንዲያይ የሚያስቸኩል የህይወት ተቋም ነው፡፡ ከሶስተኛው ፎቅ መስኮቴ ላይ ሆኜ ለመፃፍ እየሞከርኩ ነበር፡፡ እየፃፍኩ ያለሁት ስለ ፅሁፍ እና የፀሐፊዎች እጣ ፈንታ ነው፡፡
“በአሉ ግርማ በህይወት ቢኖር አይፈለግም ነበር” የበዓሉ ግርማ ተፈላጊነት ምንጭ ሞቱ ነው፡፡ ሞቱ ተራ ቢሆን ኖሮም ስነ-ፅሁፉም በተራው ተርታ ተረስቶ ይቀር ነበር፡፡ ህይወቱ እና አሟሟቱ ራሱ የልብ ወለድ አጀማመር እና ፍጻሜ እንደ አጋጣሚ ስለተላበሰ በህዝቡ ልብ ውስጥ ስሙ ታትሞ ቀረ፡፡ ህዝቡ የሚገርም ባህርይ አለው፡፡ ልብወለድ የመሰለ እውነተኛ የህይወት ታሪክን ያደንቃል፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ልብወለድን (ማለትም ታላቅ ጥበበኛ በልቀት ታድሎ ያበረከተውን የስነፀሁፍ ፈጠራ) ግን ይፀየፋል፡፡ መጸየፍ ማለት ድርሰት እና ደራሲው በአካል እና መንፈስ በመሃከላቸው እየተመላለሰ እያዩ እንዳላዩ ችላ ይሉታል፡፡ መቁጠር ይቻላል፡፡ በዚህ መልክ ችላ የተባሉትን … መስፍን ሀብተማርያም (ሰዓሊውንም ደራሲውም)፣ መንግስቱ ለማ፣ ፀጋዬ ገብረ መድህን፣ስብሃት ገ/እግዚአብሔር፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ደበበ ሰይፉ፣ ከበደ ሚካኤል …
እንዲያውም ከበዓሉ ግርማ በስተቀር ሌሎቹ በህይወት እያሉ የተረሱ በሞታቸው ምክንያት ቀብሩ እስኪያልቅ ብቻ የሚታወሱ ናቸው፡፡ ለሆነ ዓላማ ብቻ ግጥማቸው ወይንም ስነፅሁፋቸው ሲፈለግ፣ አፅማቸው ከወዳደቀበት ተለቃቅሞ ለቅፅበት የተፈለጉበት ዓላማ እስኪሳካ ብቻ ስማቸው ይጠራል፡፡ ይኸው ነው! የከበደ ሚካኤል እጣ ፈንታ የትራጀዲን ትክክለኛ ትርጉም በጥሞና እንድናሰላስል የሚያስገድደን ነው፡፡ ትራጀዲ ማለት እንደ በዓሉ ግርማ ያላመኑበትን ነገር ፅፈው ለአመኑበት ነገር መሞት አይደለም፡፡ በድንገተኛ ሞት በሰውም ሆነ በእጣፈንታ እጅ መቀጨትማ እንከን አልባ የሞት አይነት ነው፡፡ ትራጀዲ አይደለም፡፡
ትራጀዲ ማለት በቁም እያሉ መልካም አርአያ ሆነው የተሰጡለት ህዝብ .. በሆነ ባልታወቀ ምክንያት .. በወረት ቆመው እንዳሉ ሲረሳቸው ነው፡፡ ከበደ ሚካኤል ለወጣቱ ትውልድ ራሳቸውን ሲሰጡ ኖረው … ትውልዱ በቁም እያሉ ረሳቸው፡፡ ሀያ ሁለት ኬሻ መፅሐፍ በመጥረቢያ የፈለጡት ተማርረው ነው፡፡ መልካም በሰራሁ ለምን ክፉ ተመለሰልኝ ማለታቸው ነው፡፡ በወጣትነታቸው ዘመን መልካም ያሰቡለትን ትውልድ በመጨረሻ ዘመናቸው ውድቀትን ነው የተመኙለት፡፡ አስራ ሰባት አመታት ከደርግ ጋር አብሮ የረሳቸው ትውልድ ደርግ ሲወድቅ ትዝ አሉት … “ዶክተር ላድርግዎት” አላቸው- “ግድ በማይሰጣቸው ዘመን”፡፡ የእሳቸው ህይወት መቀጨት የነበረበት በጣሊያን ወረራ ዘመን ሳይሆን አይቀርም፡፡ በጣሊያን ወረራ ዘመን ቢሞቱ እንደ በዓሉ ይሆኑ ነበር፡፡ ከደራሲ የሚፈለገው የልብወለድ ድርሰቱ ሳይሆን ልብወለድ ድርሰትን በመሰለ አኳኋን ህይወቱን ማጣት መቻሉ ነው፡፡ ህዝቡ ለጥበብ ቦታ የለውም፡፡ እንደዚህ እያልኩ ምሬቴን በጠዋት ተነስቼ እየከተብኩ ነበር፡፡ ከወረቀቴ ለአፍታ ቀና ብዬ ከመኝታ ቤቴ መስኮት ወደ ደጁ ተመለከትኩኝ፡፡

የተለመደው ጭርታ ነው ያለው፡፡ የኮንዶሚኒየም ትውልድ አላማ ተኮር ነው፡፡ በጠዋት ተነስቶ ወደ ስራ ይሄዳል፤ ማታ ሳያመሽ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ማታ ራሱ ከአራት ሰዓት በኋላ መብራት የሚያበራ በእኛ ብሎክ አካባቢ የለም፡፡ ምናልባት እኔ ብቻ ነኝ እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት መጽሃፍ እያገላበጥኩ የምቆየው፡፡ ከቀኑ አራት ሰዓት ገደማ በመሆኑ ተራርቀው ከተገነቡት የኮንዶሚኒየም ህንፃዎች በስተቀር ምንም አይታይም፡፡ ድንገት ትይዩ ካለው ህንጻ ጥንዶች ብቅ አሉ፡፡ ሴቲቱ ወንዱ ክንድ ላይ ተንጠልጥላለች፡፡
ከተቀመጥኩበት ርቀት ላይ እንኳን ሆኜ ወንድየው በጣም ወጣት እንደሆነ ለየሁት፡፡ ያጠለቀው ጥብቅ ያለ “እስኪኒ” ሱሪ ስለሆነ ሳይሆን ሁሉ ነገሩ ልጅ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ የልጁ እንቦቃቅላነት የሚተኮርበት የሆነብኝ ክንዱ ላይ በተመረኮዘችው አንፃሩ ምክንያት ነበር፡፡ እሷም በእሱ እድሜ ልክ ብትሆን ትኩረትም አልሰጣቸውም ነበር፡፡ እሷ ግን የእሱ አክስት ነገር ናት፤ በእድሜ እንጂ በዝምድና አይደለም አክስትነቷ፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም፤ በእህት ልጅ እና በአክስት መሀል ያለ ግንኙነት አይደለም ያደጋገፋቸው፡፡ ያስተቃቀፋቸው የዝምድና ሳይሆን የፆታ ፍቅር ነው፡፡ የሴቷ መቀመጫ ሴቶች ወደ አደገኛው እድሜ ክልል መግባት ሲጀምሩ እንደሚሆነው ሰፍቷል፡፡ እንደዚህ ሲሰፋ ጥብቅ ያለ ታይት ቢደረግም ከደረሰበት እርከን ወደ ኋላ አይመለስም፡፡ ግን ወደ ተመረኮዘችው ወንድ እድሜ ለመድረስ የተቻላትን ሁሉ እያደረገች ነው፡፡
ወንድየው አንገቱን ወደ እሷ ዘንበል እንደማለት አድርጎ “ክርስቶስን” መስሏል፡፡

ትሁት የመሰለበትን ምክንያት በአለሁበት ሆኜ እንድገምት ለራሴ ፈቀድኩ፡፡ ወጣቶች እንደዚህ አንገታቸውን የሚያንጋድዱት ምክር መሰል ወሬ እያደመጡ ባሉበት ቅፅበት ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ሚስቱ እየመከረችው ነው፡፡ ጸጉሯን  አናቷ ላይ ወስዳ ስለቆለለችው አንገቷ ይታያል፡፡ ሳይወልዱ እድሜያቸው መሄዱ ሌት ተቀን የሚታወሳቸው ሴቶች፣ አንገታቸው ከጭንቅላታቸው እና ከትከሻቸው ጋር ከመገጣጠሙ በፊት ለምን በጣም እንደሚቀጥን ሁሌ ይገርመኛል፡፡ ጭንቅላታቸው ትንሽ በለጥ ከማለቱ በስተቀር ሰጎን ነው የሚመስሉት፡፡ የሰጎን አንገት ከግዙፍ አካሏ አንፃር እንደሚቀጥነው አክስቲቱ ሚስቱ ቀጥናለች፡፡ አረማመዷ ቀስ ያለ ነው፡፡ መኪና እንደሚስፈልጋት ታስታውቃለች፡፡ መኪና ለመግዛት ወጣቱ አልደረሰም፡፡ የእሱ እድሜ ፓርቲ በመጨፈር እና ከወንድ ጓደኞቹ ጋር ድራፍት በመጠጣት ላይ ነው ያለው፡፡ ለእሷ መኪናም ሆነ የባልነት ቀልብ ለመግዛት ገና አስር አመት ገደማ ይቀረዋል፡፡ እሷ ግን አስር አመት እሱ ቀልብ እስኪገዛ መጠበቅ አትችልም፡፡ ለዚህ መሰለኝ የምክር መትረየስ ጆሮው ላይ እያወረደችበት ያለችው፡፡ እሱ አንገቱን ጋደል አድርጎ እየሰማት ነው፡፡ ሚስቱን እና አክስቱን እየሰማት ነው፡፡ በራሱ እድሜ ተሸማቅቆ፣ በእሷ እድሜ ልክ እንዲደርስ በምክር ባቡሯ እየዳመጠችው ነው፡፡ እሱ ደግሞ እያዳመጣት ነው፡፡ “እኔ የማይሻሻል ወንድ አልወድም… ልጅ ሆነህ መቅረት ነው እምትፈልገው?! …” ምናምን እያለችው እንደሆነ ከተቀመጥኩበት ሆኜ በግምት ጆሮዬ ቁልቁል አደመጥኳቸው፡፡
በእግሯ እንደምትራመደው አይደለም … (እርግጠኛ ነኝ) በአፏ የምታወራው፡፡ እድሜ ሲጨምር ለሴቶች እግር ዝግ የሚለውን ያህል አፍ ይቸኩላል፡፡ ከአይኔ እስኪሰወሩ ተመለከትኳቸው፡፡ የሰሚት ኮንዶሚኒየም የተገነባው በሰፊው መልከአ ምድር ላይ ተንሰራፍቶ ስለሆነ፣ ከእይታዬ እስኪሰወሩ ብዙ ጊዜ ነው የፈጀብኝ፡፡ ከተሰወሩም በኋላ ስጽፍ ወደቆየሁት ምሬት መሰል ነገር በቶሎ መመለስ አልፈለግሁም፡፡ ከማማረር መዝናናት ይሻለኛል፡፡ ችክ ብዬ ስለ ስነፅሁፍ ህይወቴ ከማማርር የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎችን እያየሁ “ሙድ” ብጤ ብይዝ ይሻለኛል፡፡ ወደ ፅሁፌ ለማተኮር እየተኮማተርኩ እያለሁ፣ ምኞቴን በ “The Secret” ጽንሰ ሀሳብ የሚሰራው እግዜር ሰማኝ መሰለኝ፣ ሌላ ትዕይንት በሄዱት ፋንታ ለአይኔ ሲል ተላከልኝ፡፡ እኔ ከተሰቀልኩበት ፎቅ ስር ሁለት አዲስ ጥንዶች …ተጣምደው ተመዘዙ፡፡ እነዚህም ወጣቶች ናቸው፡፡ ጎጆ ወጪዎች፡፡ የጎጆ “ወጪው”ን ግን መቋቋም የቻሉ አይመስሉም፡፡ የሚገርመው ነገር እነዚህ ጥንዶች ደግሞ ቅድም ካለፉት ጋር ተቃራኒ ናቸው፡፡ ማለትም፤ እነዚህኛዎቹ ላይ ወንድየው አጎት ነገር ነው፡፡ ሱፍ ኮት እና ሱሪ ለብሷል፡፡ መለጥ ብሏል፡፡ ኮቱ ወደ ኪሶቹ አካባቢ ወደ ላይ ሸብሸብ ብሏል፡፡ የኮት ኪሱ ውስጥ ያለው ሳንቲም እንዳይራገፍ በግራና ቀኝ እጁ ጨብጦ፣ ባስን ሲያባርር ብዙ አመታት ያሳለፈ መሆን አለበት፡፡ ሰሚት ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎችን የምታመላልሰው ባስ “119” ነው ቁጥሯ፡፡ አሁንም ምናልባት ባሷ ወደምትቆምበት ፌርማታ ነው እነዚህ ባል እና ሚስት የሚሄዱት፡፡

ሴቲቱ ወጣት ናት፡፡ ግን ወጣት እንደሆነች እንኳን የምታውቅ አትመስልም፤ እንዳይመስላት ያደረጋት የተሸከመችው የሚስትነት ኃላፊነት እንዳይደለ ግልፅ መሰለኝ፡፡ መግፋት የጀመረው በሆዷ ውስጥ ያለው ሽልም አይደለም ወጣትነትን አስረስቶ እናትነትን አምና እንድትቀበል ያስገደዳት፡፡ ለአረማመዷ “አክስታዊነት” እንደ ጥላ ሆኖ ምክኒያት የሆናት ከጎንዋ የሚራመደው የባልዋ “አጎታዊነት” ነው፡፡ የወሬ ትንተናውን የሚያቀርበው አጎትየው ነው፡፡ አንድ እጁን እንደ መዘውር እያሽከረከረ እየገለጸላት ነው፡፡ እናት መሆኗን ለቅፅበትም መርሳት እንደሌለበት እያስረዳት ነው፡፡ ሴት በእድሜ አክስት ሆና ስትናገር ምክር ይባል ከሆነ፣ አጎት ባልን መስሎ በእድሜ ያነሰች ሚስቱን ሲመክር ደግሞ “ተግሳፅ” ይመስላል፡፡ እየገሰጻት ነው፡፡ግን ከቅድሞቹ አንጻር የአሁኖቹ ጥንዶች ሳይግባቡ እንደተጋቡ አያስታውቅባቸውም፡፡ እንዲያውም የተመጣጠኑ ይመስላሉ፡፡ ኮንዶሚኒየም የማይመጣጠኑ እድሜዎችን የማመጣጠን አቅም አለው፡፡ ኮንዶሚኒየም የሚፈልገው ነገር አነስተኛ እና ጥቃቅን አቋም ያላቸውን ተስፈኞች ማስተሳሰር ብቻ ነው፡፡

አጎትየው ባል በቅርቡ መኪና እንደማይገዛ አምና የተቀበለች ትመስላለች፡፡ ባስ ወደ መጠበቂያው አብረው ያመራሉ፡፡ ሁለቱ ጥንዶች ወጣቶች አብረው ፓርቲ ቢሄዱ፣ ሁለቱ አጎት እና አክስትየዋ ደግሞ ቤት ዘግተው ቢመካከሩ… ከኮንዶሚኒየም እስር ቤት የመውጫ  መፍትሄ መዘየድ በቻሉ ነበር .. ስል አሰብኩኝ፤ ከፎቅ ወደ መሬት እየተመለከትኩኝ፡፡ እነሱ ከመሬት ወደ እኔ ቢመለከቱ ምን እንደሚያስቡ አላወቅሁም፡፡
ወደ ፅሁፌ ተመለስኩ፡፡ “ያልተመጣጠነ ጋብቻ ትራጀዲ ነው፡፡ ህዝብ እና ደራሲ የሚያደርጉት ጋብቻ እኛን በመሰለችው ሀገር ትራጀዲ ነው፤ ህዝብ በእድሜ የገፋ ገሳጭ እና መካሪ ቀጪም ነው፡፡ መቅጣት የነበረበት ግን በተገላቢጦሹ ደራሲው ነበር፤ ደራሲው ህዝብን መምራት ነው እንጂ ያለበት በተገላቢጦሹ ትራጀዲ ነው፡፡ የደራሲው መንፈስ የወጣት ብሩህ መንፈስ ነው፡፡ የህዝብ መንፈስ አሮጌ እና መሻሻልን የማይሻ ነው፡፡ በዚህ ጋብቻ ውስጥ ተጨቁነው የሞቱ አያሌ ደራሲዎች አሉን፡፡ … የሞታቸው ጊዜ በረዘመ ቁጥር ደግሞ ትራጀዲው በሰማይ እና መሬት መሀል ያለውን የእጣ ፈንታ አስከፊነትን መላልሶ የሚያረጋግጥ ይሆናል…”
እያልኩ ብዙም መቀጠል አልቻልኩም፡፡ ማሰብ የምፈልገው የኮንዶሚኒየሞቹን ጥንዶች ሆኖ ሳለ፣ ስለ ስነፅሁፍ ቅሬታ እንዲሰማህ  አድርገህ ፃፍ ብሎ ያዘዘኝን አካል በማማረር ለረጅም ሰዓታት ተቀምጬ ቀረሁ፡፡ መስኮቱ ሀሳቤን ስለሚበታትነው ብጋርደው ተሻለኝ፡፡ ጋርጄ በደብዛዛ ብርሀን፣ ስለ ደብዛዛው የስነጽሁፍ አለም እጣ ፈንታ ለመጻፍ ማማጤን ቀጠልኩ፡፡     

Published in ጥበብ
Monday, 06 October 2014 08:15

ማራኪ አንቀፅ

          ከአዋሳ እርሻ ኮሌጅ በዲፕሎማ ከተመረቅሁ በሁዋላ እዛው ከተማ 75 ዓመተምህረት ላይ በማውቀው ሰው እርዳታ ግብርና ሚኒስቴር ተቀጠርኩ፡፡ ‘አዲስ አበባ እንመድብሽ’ ቢሉኝም አልሄድም ነበር፡፡ አዲስአባን ጠላሁዋት፡፡ በቦዲ ሚሞሪ (የገላ ትውስታ ወይም የገላ ትዝታ) ይመስለኛል፡፡ ቦዲ ሚሞሪ (Body Memory) በአንጎል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌላ የአካል ክፍል ውስጥም (በጡንቻ፣ በልፋጭ፣ በሞራ፣ በጉበት፣ በሳንባ ወዘተ) ትውስታ ሲከማች ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ ጉዳዩ ከሽሮሜዳው አላዛር ጋር ተደርቦ አዲስአባን ስጠላ ትንሽ ልክ አይደለም፡፡ ባቡር ጣቢያ ምን አደረገኝ? በቅሎ ቤትና መካኒሳ ምን አደረጉኝ? እናቴ ለምን አዲስአባ እንደማልመጣ ስትጠይቀኝ  “እማመጃ ሙች መንግስት በእጣ ልመድብ እያለ አዋሳ ደረሰኝ፤ ገንዘብ ከፍዬ እንኳን የሚለውጠኝ አላገኘሁም፡፡ ምስክር ካስቸገረችሽ በደንብ ስቋቋም እወስዳታለሁ” አልኳት እማማ ‹ኸረ ለልጅቷ አይደለም፤ በሰራተኛ ከምታድግ ከእኔ ጋ ትሆናለች፡፡

ይሄን ደርግ የተባለ በጥባጭ ማን ላከብን እመቤቴ› ምናምን ምናምን፡፡ በልቤ የፈለግሽውን በይ እላለሁ፡፡ የአገራችን ምስክር መሃላ ነው፡፡ እንዋሽና እንምላለን፡፡ የማንምልበት የለም፡፡ ልብ ያልኩት እንዲህ ስገባበት ነው፡፡ በእግዚአብሔር እንምላለን፤ በሃይለስላሴ እንምላለን (ከንጉሠ ነገሥቱ የሚቀረው ጢማቸው ነው፣ እና ቀን ጠብቀንም ከተመቸን በጢማቸውም እንምላለን)፣ በመላእክት፣ በአባት፣ በእናት፣ በምንወደው ሰው፣ በደርጉ፣ በልባችን፣ በሳንባችን፣ በባላችንና በሚስታችን እንምላለን፡፡ በዚህ በዚህ ተለማምጄ ምናልባት በፋሲል እምላለሁ፤ በፋሲል ፔርሙስም እምላለሁ፡፡ ወደ አዋሳ ለመሄድ አንዳንድ እቃዎቼን በሻንጣ ስከት ያገኘሁዋቸውን የማርኪሲስት መፅሀፍት ለማድቤት እሳት ወረወርኩ፡፡ እስር ቤት ሙላት የሰጠኝን ያማረች ቅል እንዳትሰበርብኝ በጥንቃቄ በወረቀትና በላስቲክ ጠቅልዬ በልብሶቼ መሃል ወሸቅሁዋት፡፡ ድሮ አበባና ተክሎችን ከሰበሰብኩባቸው ሶስት አልበሞቼ አንዱን ብቻ አገኘሁ፡፡

ታስሬ ከተወሰድኩ በኋላ በበነጋታው ፈታሾች እኔን የሚወነጅሉበት ጸረ-አብዮት ወረቀት ሊያገኙ ሲበረብሩ እንደነበር ተነግሮኛል፡፡ የቀሩትን በርባሪዎቹ እንደወሰዱአቸው አውቃለሁ፡፡ ቢያበሳጭም ምን ይደረጋል? “ምን አውቃለሁ የሆነ ወረቀት ሰብስበው ሄዱ” አለች እማማ፤ ቀኑ ሲያልፍ፡፡
አላለፈም፡፡ በልጅነቴ የለፋሁበት ሲጠፋ ሃዘን አይገባኝም አሉ? ሃዘን ካለ የአልበሞቼ ትዝታ አለ ማለት ነው፡፡ ሁሉም አልበሞቼ ገና እኔ ውስጥ አሉ፡፡ ትንሽ ተቀምጬ ከትውስታዬ ሊጠፋ የጀመሩ አትክልቶችን እየገለጥኩ አየሁ፡፡ የመፅሀፉ ጠረን መስከረም ወር ውስጥ እንደሚያጋጥም የእንጦጦ ሸለቆ ነው፡፡ መጨረሻው ገፅ ላይ አንድ ጠጅ ሳር አገኘሁ፡፡ ገና በጣቴ ስነካካው ፈራረሰ፡፡ መደርደሪያዬ ላይ ደሞ ምናልባት ከሰባት አመታት በፊት አላዛር ለልደት ቀኔ የሰጠኝን አንድ ዳልሜሽያን የውሻ አሻንጉሊት አገኘሁ፡፡ ወደ ግድግዳ ገፋ ተደርጋለች፡፡ አቧራ ለብሳለች፡፡ በአዲስነቷ በጥቁር ነጠብጣቦች የተሸፈነች በረዶ ነጭ ነበረች፡፡ አይኖቿ ጥቁር ሆነው በዙሪያቸውን አረንጓዴ ናቸው፡፡ አፍንጫዋ ጥቁር ነው፡፡ ጅራተ ጎራዳ ናት፡፡ አልጋዬ ላይ በጀርባዬ ስሆን ሳታቋርጥ ታየኝ ነበር፡፡ አስተያየቷ ያባባል፡፡ ቆሻሻዋን አራግፌ ሻንጣዬ ውስጥ ከተተትኳት፡፡
አቶ አባይ አዋሳ አደርሳታለሁ ስላሉ ሳሎን ተቀምጬ እሳቸውን ስጠብቅ ቆይቼ፣ ሰልችቶኝ መኝታ ቤት ስገባ፣ እማማ ሻንጣዬን ስትበረብር አገኘሁዋት፡፡ በቀኝ እጅዋ ዳልሜሽያን አሻንጉሊቷን ይዛለች፤ ቀና ብላ በማዘን አየችኝና ምንም ሳትናገር እነበረችበት አመቻችታ አስቀመጠቻች፡፡ አፍሬ ወደ ሳሎን ተመለስኩ፡፡ አለሁበት መጥታ ምንም ነገር እንዳልሆነ፡፡
“አባይ የት ጠፋ? እያረጀ ሲሄድ ቀጠሮ መርሳት ጀመረ?” አለች፡፡ አልመለስኩላትም፡፡
አጠገቧ እግሮቿ ስር በጉዞዬ አውቶቡስ ውስጥ የምበላቸው ብርቱካኖች ሙዞች ተደጋግፈው ተቀምጠዋል፡፡ ብርቱካኑ ቅጠልያ ቀለሙ አልተወውም፡፡ ሎሚ አስተኔ ቆምጣጣ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ፍራፍሬ ኮርፖሬሽን ቤመንገዱ ድንኩዋን ተክሎ ኪሎው በሁለት ብር ካምሳ ከሚሸጠው ከእማማ ገዝታ ነው፡፡ ከነዚህ ጎን ደሞ ገና አረንጓዴነቱ ያለቀቀው ጥሬ ሙዝ አለ፡፡ እማማ ከመስሪያቤቷ ስትወጣ፣ የስራ ጓደኛዋ ልጅሽን ደህና ግቢ በይልኝ ብላ የላከችልኝ ነው፡፡ ከሴትዬዋ አልቀራረብም፡፡ ሙዞቹ ጥሬ ከመሆናቸው የተነሳ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጠንከራ ሰረሰሮች አሉዋቸው፡፡ ስድስቱም አንድ አንጓ ላይ እንደ ደራጎን ጥርስ ተደርድረዋል፡፡
እማማ የላስቲክ ቀረጢቱን በእግሯ እየነካካች ታስባለች፤ ስለ እኔ ጉዞና ሰፈር ስለመቀየር ይሁን ስለ አባይ እንጃ፡፡ እኔ መሄዴ ነው፡፡ እማማ ብቻዋን መኖር የምትችል አይመስለኝም፡፡ ከአባይ ጋር ለምን እንደማይጋቡ አይገባኝም፡፡ አሻንጉሊቴን ባታይብኝ ኖሮ ትዳር ስለመመስረት እጠይቃት ነበር፡፡ ግን፤“አንቺስ አሻንጉሊት ከመሰብሰብ አላዛርን ጠበቅ አታደርጊም ነበር” ብትለኝስ ብዬ ተውኩት፡፡ በየቀኑ በደም ስሬ፣ በልቦናዬ ደካማ የሚያደርገኝን ነገር የምሰበስብ ይመስለኛል፡፡----
(ከደራሲ አዳም ረታ
መረቅ የተሰኘ አዲስ ረዥም ልብወለድ
መጽሃፍ ውስጥ የተቀነጨበ፤2007 ዓ.ም)

Published in ማራኪ አንቀፅ

               ኮሚቴ ጥሩ ነው፡፡ እቃ ቢጠፋችሁ፣ ታናሽ ወንድም ቢያናድዳችሁ፣ እቴቴ ከማለት ኮሚቴ ማለት ብልህነት ነው፡፡ ኮሚቴ ውሀን ከጥሩ፣ ነገርን ከስሩ ስለሚፈትሽ፣ በሰብሳቢው ወንበር ጐማና በነገሩ ብልት አላማ ላይ እየተሽከረከረ ጥሩ አድርጐ ስራን ያጓትታል፡፡ በፋይል ላይ ፋይል ይከፍታል፡፡ በመጨረሻም ጊዜያችሁን ለመቆጠብ፣ እንባችሁን ላለማንጠባጠብ በሚል ጉዳያችሁን ለሌላ ኮሚቴ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ እና ኮሚቴ ጥሩ ነው፡፡ ኮሚቴ ውደዱ
በህይወት ሩጫ፣ በኑሮ ትግል ፍጥጫ ውስጥ ግባችሁ ማሸነፍ ከሆነ፣ በዚህም አለም በወዲያኛውም አለም ኮሚቴ ይኑራችሁ፡፡ ኮሚቴ ያላቸው አረመኔ ቢሆኑ ፃድቃን፣ ተራዎች ቢሆኑም ልሂቃን ናቸው፡፡ ሲያጠፉ እየታለፉ፣ ሲዘርፉ እየታቀፉ፣ ሲንዘላዘሉ እየተደላደሉ ይቀጥላሉ፡፡ ሰማይ ቢታመስ፣ መሬት ብትርመሰመስ ቅጠላቸውን ነፋስ፣ ግንዳቸውን ፋስ አያገኘውም፡፡ ኮሚቴ ከሌላችሁ ጉዳችሁ! ምን አመል ምን ሽመል፣ ምን ፍሬ ምን ጥንካሬ ቢኖራችሁ፤ ምን አዋቂ ምን አስደናቂ፣ ምን ጉደኛ ምን አስማተኛ ብትሆኑ፣ ራሳችሁን ትደፉ እንደሆነ እንጂ ሚዛን አትደፉም፡፡ ስለምታሳዩት ጐዳና፣ ስለምትለግሱት ፋናም እንቸብችብህ እንጂ ግዛን፤ እናጥቁርህ እንጂ አውዛን የሚላችሁም አታገኙ፡፡ እንደውም ስትባትሉ ልታስመስሉ፣ ስትታትሩ ልትቆነጥሩ፣ ስትማልዱ ልትቀልዱ ይሆናል፡፡ ስብሰባ ስትቀመጡ አለቃ ልታንጓጥጡ፣ አስተያየት ስትሰጡ ልታሳጡ፣ ፍትሀዊነትን ስታሞካሹ ስራ ልታበላሹ፣ መብት ስትጠይቁ ሰራተኛ ልትነቀንቁ ነው፡፡ እና ኮሚቴን ውደዱ፡፡ ኮሚቴን አትለፉ፤ ኮሚቴ ከሚያልፋችሁ ጡቷ እንደበሬ ቀንድ የተገተረ የገለጠች ኮረዳ ብታልፋችሁ ይሻላል፡፡
በበኩሌ በሌላው ህይወቴ የገጠመኝን እክል፣ የደረሰብኝን መሰናክል ስለማውቀው አኗኗሬ ብቻ ሳይሆን አሟሟቴም በኮሚቴ ይሆን ዘንድ ተናዝዣለሁ፡፡ ለኮሚቴ እስከባህር አንጀቴ የጠለቀ፣ እስከ ልቤ ገበር የዘለቀ አክብሮትም አለኝ፡፡ ቀን ወደ ርስቴ፣ ማታ ወደ ሚስቴ ስሄድ፤
ኮሚቴ ኮሚቴ
ግባ ወደ ቤቴ
ና ወደ ህይወቴ
እንቅልፍ ጥሩ ነው ለሰውነት ድካም
ግን እንደ ኮሚቴ አይገኝም መልካም
አስቤ ከስቤ ያልሞላልኝ ኑሮ
እድሜ ለኮሚቴ ሆነልኝ ዘንድሮ
እንግዲህ አልክም ገብሬልን ወደ አምላክ
ከስሬ  አገኘሁት የኮሚቴን መላዕክ፡፡
ስል የማንጐራጉረውም ይህንኑ አክብሮቴን ለመግለጽ ነው፡፡ መቼም ውጭ ነቀል፣ ሀገር በቀል የሆነው ኮሚቴ ግራ ቀኙን አይቶ፣ ደንብና ስርአቱን ተመልክቶ በየጊዜው ለሚያቀርብልን ፈተና፣ ያለ ስስት ለሚነፍገን ቅልጥፍና አክብሮት ቀርቶ አምልኮት አይበዛበትም፡፡ እስኪ እናንተም የኮሚቴ ፍቅሩ እንዲያድርብን፣ ፀጋው እንዲራገፍብን በምትሰሩበት መስሪያ ቤት አልያም በተከራያችሁበት ቤት ውስጥ በሰሪውና በአሰሪው፣ በአስኗሪውና በኗሪው መካከል ኮሚቴ ያለውን አስተዋጽኦ አጋሩን፡፡
እኔ በምሰራበት አንድ የግል ተቋም ውስጥ ለመልካም አስተዳደር የሰራተኞችን ቅሬታና አቤቱታ ይዞ በአሰሪዎች ፊት የመቆምና ክፍተቶችን የመጠቆም አላማ ታጥቆ የተመሰረተ የሰራተኞች ተወካይ ኮሚቴ አለ፡፡ የዚህ ኮሚቴ አባላት በዝና ከሰራተኛው፣ በዝምድና ከአስተዳደሩ የሆድ ዕቃ የሚቀነጣጠቡ ጉበቶች ሲሆኑ ግብራቸው ከሰራተኛው የሚመነጩና ሃላፊዎችን የሚያግረጨርጩ አዳዲስ አስተሳሰቦችን መርዛማነት መቆጣጠር ነው፡፡ አስተሳሰቦቹ ለአለቆች ስልጣን ገደብ፣ ለሰራተኛው ባርነት ወደብ የሚያበጁ የመብትና የዕውነት፣ የልቀትና የእውቀት ጥያቄዎች ሆነው ሲያገኟቸው እንደ ጠላት መንጋ፣ እንደ የዕሳት አደጋ ባሉበት ከበው በደረሱበት ተረባርበው ያዳፍኗቸዋል፡፡ በነሱ ግምት ብዙኃኑን ሳይገዙ፣ ንፁሀኑን ሳይበርዙ፣ ቂላቂሉን ሳያነቁና ሆዳሙን ሳያስጠነቅቁ ያከስሟቸዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ አምልጦ በየግንኙነቱ አቆጥቁጦ፣ የአመራሩን ክፍተት፣ የስራ ሂደቱን አተት በመዘርዘር ሙስናን የሚያሳጣ፣ ልግመኞችን የሚቀጣ ነገር ግን ተቋሙን ከጉድ የሚያወጣ ሃሳብ ከተገኘ ደግሞ የሃሳቡን በኩር አቀንቃኞች ነቅሰው፣ ተከታዮቻቸውን አግበስብሰው፤ ገሚሱን ከስራ ቦታ፣ ቀሪውን ከዕድገት ኮታ በማፈኛቀል የተቋሙ ነባር የተፈጥሮና የእሮሮ ሚዛን ባለበት እንዲቀጥል ይተጋሉ፡፡ እንግዲህ የሰራተኞች ተወካይ ኮሚቴ ልክ እንደ ማንኛውም አይነት ዝነኛና ዘገምተኛ ኮሚቴ ንቦችን ረግጦ፣ አንበጣዎችን አስበልጦ የግልና የጋራ ህልውናን እንደ አሮጌ መኪና የሚያንገታግት፣ እንደ ወደቀ ፈረስ የሚጐትት፤ ጥቅሙ የላቀ፣ አገልግሎቱም የጠለቀ ኮሚቴ መሆኑ ነው፡፡
እና ኮሚቴን ወደዱ፡፡ በኮሚቴ መሳተፍ፣ በኮሚቴ መንተፋተፍ ልመዱ፡፡ ኮሚቴ ኑሮ ነው፤ ኮሚቴ ጉሮሮ ነው፡፡ ኮሚቴ የገነት በር፣ የኤሌትሪክ ወንበርም ነው፡፡ ኮሚቴ ዛሬ የምንጠይቀው ዕድገት፣ ነገ የምናጐነብስበት ስግደት፤ አሁን የምንቆርጠው ስጋ፣ ኋላ የሚደገስልን አደጋ ነው፡፡ ኮሚቴ ተገፍተን የምናልፍበት፣ ተሸንፈን የምንረታበት፣ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ነው፡፡ ኮሚቴ ሁሉም ነው፡፡ ኮሚቴ ኮሚቴ ነው፡፡ ኮሚቴ በቤት ይሁን በጐረቤት፣ በሰፈር ይሁን በጠፈር፤ ጊዜና ቦታ፣ ዕድሜና ፆታ፣ ብሔርና እግዜር ሳይለይ የሰው ልጆች ሁሉ በተሰማሩበት ፊና፣ በሚኖሩበት ቀጠና ውስጥ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ፣ ተጽዕኗቸውን ለማጥበቅ በተጨማሪም ምድር የፍሪዳ ብቻ ሳትሆን የፍዳ ገበታም መሆኗን ለማስተማር የሚገለገሉበት ተቋም፣ የሚራቀቁበት አቋም ነው፡፡ ይህን ተቋም አቋቋሙ፡፡ ይህን አቋም አጠራቅሙ፡፡
አነሰም በዛ፣ አማረም ጠነዛ ኮሚቴ ለምትከውኑት ስራ፣ ለምትመኙት ጉራ፣ ለምትመሰርቱት ዕድር፣ ለምታሰለጥኗት ምድር፣ ለምታሳድጉት ልጅ፣ ለምታፈርጡት ብጉንጅ፣ ለምታዘጋጁት ስጦታ፣ ለምታቀርቡት ስሞታ፤ ለምትነፉት መለከት ፣ ለምታራምዱት አመለካከት ወሳኝ ነው፡፡ እያንዳንዳችን በኑሮ መልክ፣ በዕድሜ ተረክ ስንቀርብ የምንገለጽባቸው ቁም ነገርና አሌ፣ እውነትና ሀሰት፣ ቅንነትና ቂልነት፣ ደግነትና ክፋት፣ ልማትና ጥፋት የመሳሰሉት መስፍሪያ ባህርያት የኮሚቴ እይታዎች ስለሆኑ ለመነሳት ወይም ለመረሳት የኮሚቴ ደንታ፣ የኮሚቴ ይሁንታ ያስፈልጋል፡፡
የኮሚቴ ስጋዊ አስተምሮ፣ መንፈሳዊ ተከራክሮ ተገልጦላቸው በጥላው ስር የፈሰሱ፣ በቪላው ውስጥ የተኮፈሱ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በገድላቸው የሚነግሩን፣ በስንክሳራቸው የሚያስተምሩን ይሄንን ነው፡፡ ኮሚቴ ሲያጥሩ ቁመት፣ ሲሻሩ ሹመት፣ ሲወድቁ ዘብ፣ ሲየጡ ገንዘብ እየሆነላቸው ይለመልማሉ፡፡ ቅጥፈታቸው እውነትን፣ ነውራቸው ጌትነትን ይገበይላቸዋል፡፡
ቁጭ ብለው ሀኖስ፣ ተኝተው ውቅያኖስ ስለሚረግጡም ለዙሪያቸው ፈሪና ተለማማጭ፣ አድማጭና አላማጭ ሞልቷቸዋል፡፡
ለኮሚቴ ህይወት ያልታጩ፣ ደጅ ቆመው የሚቁለጨለጩት ግን ቢያለቅሱ ሰሚ፤ ቢያብቡ ቀሳሚ፣ ጉንጭ ቢያቀብሉ ሳሚ የላቸውም፡፡ በኮሚቴ እምነት፣ የኮሚቴ ሰውነት ስለሌላቸውም ንክ እንጂ ልክ፣ ከንቱ እንጂ አንቱ አይባሉም፡፡
እጆቻቸው የቅሬታ ደብዳቤ ሲያረቁ፣ ልቦቻቸው አንድ ምላሽ እየናፈቁ ይኖራሉ እንጂ ከኮሚቴው የሚላክላቸው ሆሄ፣ የሚሰጣቸው መፍትሔ የለም፡፡ እንዲያው በሲቃ እንዲያው በጥበቃ ይባዝናሉ፡፡
እስካሁን በክርስቶስ እድሜ ኖሬ፣ በማጅላን መርከብ ዞሬ በደረስኩበት አውራጃ፣ በተራመድኩበት ስጋጃ፣ ባየሁትና በሰማሁት ኮሚቴ አይነቱ የበዛ፣ ሃላፊነቱ የተንዛዛ ይሁን እንጂ ንዑስ ምግቡ፣ አብይ ግቡ ፈጣሪዎቹን ማገልገል፣ አማኞቹን መሸንገል ነው፡፡
 በመሆኑም በፊቱ ከቀረበለት ገበቴና ከሰብሳቢው ፎቴ ማዶ ያሉ ትዕይንቶች አይማርኩትም፡፡ ነዳይ ቢያፋጫ፣ ባለ ጉዳይ ቢንጫጫ ደንታ የለውም፡፡ የግፍ መብዛት፣ የፍትህ ርዛት የሚወልደውንም ዋይታ ወፎች ለንጋት፣ ጅቦች ለመውጋት በሚጮሁበት የተፈጥሮ ክበብ ውስጥ እንደሚፈጠር ማንኛውም አይነት ድምጽ በቸልታ ሰምቶ፣ በዝምታ ተኝቶ ያሳልፈዋል፡፡
እና ኮሚቴን ውደዱ፣ በኮሚቴ ተጠመዱ፤ ስለ ኮሚቴ ራሳችሁን ካዱ፡፡ ኮሚቴ የማያልፍበት ስንጥቅ፣ የማይገባበት ትንቅንቅ የለምና በምትሰቀሉበት ማማም ይሁን በምትከሰከሱበት አውድማ፣ በደንብ ለመኖርም ሆነ በደንብ ለመሞት ኮሚቴ ይኑራችሁ፡፡

Published in ህብረተሰብ
Monday, 06 October 2014 08:13

እንቆቅልሽ?

ወደታች የሚወርድ፣ ወደላይ ግን የማይወጣ?
በወጣትነቴ ረዥም ነኝ፡፡ ሳረጅ አጭር እሆናለሁ፡፡ ማን ነኝ?
የሜሪ አባት አምስት ሴት ልጆች     አሏቸው፡፡ ናና፣ ኔኔ፣ ኒኒ፣ ኖኖ ይባላሉ፡፡ የአምስተኛዋ ልጃቸው     ስም ማነው?
ካለኝ ለሰው አላካፍለውም፡፡ ለሰውካካፈልኩት አይኖረኝም፡፡ ምንድነው?
ሰውየው ከባድ መኪና እየነዳ ነው፡፡ የፊት መብራት አላበራም፡፡ ጨረቃም አልወጣችም፡፡
ከፊት ለፊቱ አንዲት ሴት መንገድ ታቋርጣለች፡፡እንዴት አያት?

====================


መልስ
ዝናብ
ሻማ
ሜሪ
ምስጢር
ብሩህና ፀሐያማ ቀን ነበር

Published in ህብረተሰብ

(የወላይታ ምሳሌያዊ አነጋገር)

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ዶሮና አንድ አውራ ዶሮ ወደ አንድ ፍሬ ወደ ሚገኝበት ተራራ ይወጣሉ፡፡ አንድ ስምምነት እንዲያደርጉም መነጋገር ጀመሩ፡-
አውራ ዶሮ ---------- እመት ዶሮ
እመት ዶሮ ---------- አቤት አያ አውራ ዶሮ
አውራ ዶሮ ------- አንድ ነገር እንስማማ
እመት ዶሮ -------- ምን አሰብክ ወዳጄ?
አውራ ዶሮ -------- ምንም ዓይነት ፍሬ ብናገኝ አንዳችን ላንዳችን እናካፍል
እመት ዶሮ ----- በሃሳቡ እስማማለሁ፡፡ ድንቅ መርህ ነው!
በዚህ ስምምነት ፀንተው ያን ተራራ ተያያዙት፡፡ ከሰዓታት በኋላ እመት ዶሮ አንድ ትልቅ ፍሬ አገኘች፡፡ ግን ስለማግኘቷ አንዲትም ቃል ትንፍሽ ሳትል መንገድ ቀጠለች፡፡ አንድ አሳቻ ቦታ ስትደርስ፣ ዘወር ብላ ፍሬውን ልትበላ ሞከረች፡፡ ሆኖም ፍሬው በጣም ትልቅ በመሆኑ አልዋጥ አላት፡፡ አንቆ የሚገላት መስሎ ስለተሰማት፣ በጣም ደነገጠች
“አያ አውራ ዶሮ! አያ አውራ ዶሮ!” ስትል ጮኸች፡፡
አውራ ዶሮም፤ “ምነው? እመት ዶሮ ምን ሆንሽ?” አላት፤ ካለበት ሆኖ፡፡
“እባክህ ትን ብሎኝ ልሞት ነውና ውሃ ፈልገህ አምጣልኝ”
አውራ ዶሮው በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ የውሃ ጉድጓድ ሄዶ፤ “ጉድጓድ ሆይ! እባክህ እመት ዶሮ ልትሞትብኝ ነውና ትንሽ ውሃ ስጠኝ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ጉድጓዱም፤ “መስጠት እሰጥሃለሁ፡፡ ግን በመጀመሪያ ከዕለታት አንድ ቀን የአፌ መሸፈኛ የሆነውን ቀይ ሀር ጨርቅ፣ እመት ዶሮ ሰርቃ ወስዳብኛለችና ከጌታዋ ቤት ሄደህ አምጣልኝ” አለው፡፡
አውራ ዶሮው አሁንም የዶሮ ጌታው ዘንድ እየበረረ ሄዶ፤
“ጌታዬ፤ እመት ዶሮ በውሃ እጦት ልትሞት ቢሆን፤ ጉድጓድን ውሃ ስጠኝ ልለው ሄድኩ፡፡ እሱም ወደ ጌታዋ ዘንድ ሄደህ የሰረቀችኝን ሀር አምጣ አለኝ፡፡ እባክዎ ሀሩን ይስጡኝና ውሃ ላግኝላት?” ሲል ጠየቀው፡፡
ጌትዬውም፤ “በመጀመሪያ ከቤት ሰርቃ የወሰደችውንና ለዶሮ ጠባቂው የሰጠችውን ሰዓት አስመልስልኝ” አለው፡፡
አውራ ዶሮ ሲበር ሄዶ ዶሮ ጠባቂውን ለመነውና ሰዓቱን አስመልሶ ለጌትዬው መለሰ፡፡ ቀዩን ሀር ተቀብሎ ለጉድጓዱ ሰጠ፡፡ ውሃውንም ከጉድጓዱ ወስዶ ለዶሮዋ ሊሰጥ ወደ ተራራው ወጣ፡፡ እዚያ ሲደርስ ግን እመት ዶሮ ለአንዴም ለሁሌም አሸልባለች፡፡
                              *           *         *
አበው “ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል” ይላሉ፡፡ አንድም ደግሞ “ሥራ ለሰሪው እሾህ ለአጣሪው” ይላሉ፡፡ የሰራነው ሥራ እስከ እለተ ሞታችን ድረስ ይከተለናል፡፡ እያንዳንዷ ዱካችን የማታ ማታ ተከትላ ታጋልጠናለች፡፡ የሙስና የመጨረሻ ፍፃሜ እንደዶሮይቱ በተያያዘ ጥፋት ዋጋ መክፈል ነው፡፡ Domino effect እንዲሉ ፈረንጆች፡፡ አይታወቅብኝ በሚል በአልጠግብ ባይነት በአሳቻ ቦታና ሰዓት የመነተፍነው የህዝብ ንብረትና ንዋይ፣ አንድ ቀን ክፉ ቦታ ላይ እንደሚጥለን እንገንዘብ፡፡ ቃልን ማፍረስ፣ የሀገርን ሀብት መበዝበዝ፣ የሀገርን ክብር ማዋረድ፤ ሁሉም ዓይነት ሙስናዎች የማታ ማታ ያስጠይቃሉ፡፡
የተጠርጣሪዎች መብዛት፣ ከስራ መባረሮች፣ የጥርጣሬና ፍርሃት መንገስ፣ ከተሾሙበት ስልጣን መባረር መብዛት ወዘተ ሁሉም የሙስና መገለጫዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የተገለጠ ዐይን ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ለማስተካከል አንጋረ ፈላስፋ የሚለንን ማዳመጥ መልካም ነው፡-
“ንጉሥ ሦስት ነገሮችን ገንዘብ ማድረግ ይገባዋል፡-”
1ኛ/ ዐዋቂዎቹን አክብሮ መያዝ
2ኛ/ ለተቸገሩት መስጠትና በማናቸውም መርዳት
3ኛ/ ህዝቡን በቅንነትና በርህራሄ ማስተዳደር፡፡”
    ቀጥሎም እንዲህ ይለናል፡-
“ብልህ ዐዋቂ ሰው፣ አንደበቱ የልቡ አማካሪ ነው፡፡ መናገር ሲያምረው አስቀድሞ በልቡ ያወጣ ያወርድና፣ ለመናገር መንገድ ሲያገኝ ይናገራል፣ ባያገኝ ግን ዝም ይላል፡፡ ቁም ነገሩ ይኸው በጎውንና ክፉውን ለይቶ መናገር ነው” ስለዚህም ነው የሙስናን ጣራ መንካት ደጋግመን ስንናገር የከረምነው፡፡ ዛሬም ያንኑ የሙስና መንገድ የሚከተሉ አያሌ ናቸው፡፡ የሌሎች መጠርጠር፣ የሌሎች መታሰር የማያስደነግጣቸው አያሌ ናቸው፡፡ የሚሰነዘረው በትር የማቀፍ ያህል ፈገግ የሚያሰኛቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
“ጉርሻ የለመደች ሴት በጥፊ ሊመቷት እጅ ሲያነሱ አፏን ትከፍታለች፡፡” የሚለው የወላይታ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡
ኢድ ሙባረክ!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንዴት ነው የአዲስ ዓመት ዕቅድ…‘ተጀመረ’ እንዴ!
እኔ የምለው…ሱስ ምናምን ነገርን በተመለከተ፣ በፊት እኮ አሪፍ ነበር፡፡ ወይ “መጠጥ አቆማለሁ…” ነው ወይ “ማጨስ አቆማለሁ…” አለቀ፡፡ አሁን ሱሶቻችን በአይነትና በብዛት ስለበዙ…አለ አይደል… እነ “መጠጥ አቆማለሁ…” “ማጨስ አቆማለሁ…” ኦልድ ‘ስቶሪ’ ነገር ሆነዋል፡፡ እኔ የምለው…ሰዋችን ይጠጣዋል! እንደምናየው ከሆነ ማጨስና መጠጣት…የሚያስተዛዘቡ መሆናቸው ቀርቷል፡፡
ደግሞላችሁ… ‘ሴሌብሪቲ’ የመሆን ሱስ አለላችሁ፡፡ …ብቻ እንደምንም ብለን ወይ ‘ሲንግል’ ለቀን ዘፍነን፣ ወይ የሆነ ፊልም ላይ እንደ ‘ዘብ’ ለመጫወት ‘ካስት ተደርገን’ (ቂ…ቂ…ቂ… ሊያመልጠኝ ሲል መለስኩት፣)  የሆነ ኤፍ.ኤም. ላይ… “የዛሬው እንግዳችን በቅርቡ የፈልም ዓለምን የተቀላቀለው አርቲስት….” መባል የሱስ ያህል ሆኖብናል፡፡
ልጄ ሆሊዉድ እኮ ገና ሰው ዓይን ለመግባት እንኳን ስንትና ስንት ዓመት መፍጋት አለ፡፡ እንደዛም ሆኖ ዕድሜ ልካቸውን ተውነው፣ አይደለም ተመልካች ሊሰለፍላቸው፣ ዳይሬክተሮች  የማያውቋቸው መአት ይኖራሉ፡፡ እኛ ዘንድ ግን እንደዚህ አይነት ችግር የለብንም፡፡ ‘ሴሌብሪቲ’ ለመሆን ‘ትሪለር’ በሚባል ዘፈን ዓለምን መቀወጥ፣ ‘ትዌልቭ ይርስ ኤ ስሌቭ’ የሚባል ፊልም ላይ ሠርቶ ዓለምን ቁጭ ብድግ ማሰኘት አያስፈልገንም፡፡ ‘ሲንግል’ ለቃቂና ሙሉ አልበም ያወጣ እኩል ታዋቂ የሚሆኑባት አገር ነች፡፡  
እናላችሁ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ለምሳሌ የሆነ የሰፈር ልጅ ምናምን አለ፣ ሲዞር ውሎ የምሳ ሰዓቱን በምንም አይነት የማያሳልፍ አለ፡፡ እናላችሁ… እናቱ ግራ ይገባቸውና ምን ይሉታል መሰላችሁ…“እንዲሁ ሰፈር ውስጥ ስትንገላወድ ከምትውል እንደ እኩዮችህ አንድ ነጠላ ዜማ እንኳን ማውጣት ያቅትሀል!” ይሉታል፡፡ በቃ…ሲንግል ያወጣል፡፡ ሲንግል ለመልቀቁ የምታውቁት ደሞ ወይ ጸጉር ‘ፍሪዝ’ ያደርጋል፣ ወይም ሱሪውን ‘ዝቅ’ ያደርጋል!
እሷዬዋ ደግሞ ምን አለፋችሁ እየተኳኳለች፣ እየተበጣጣረች…ስትወጣና ስትገባ እናት የሰፈር ወሬ አላስቀምጥ ይላቸዋል፡፡ “ኸረ ልጄ እኔንም የቡና መጠጫ አታድርጊኝ…ምን አለ እንደ ጓደኞችሽ አንዱ ፊልም ላይ ሌላው ቢቀር ቡና ስትቀጂ እንኳን ታይተሽ የአርቲስት እናት ብታሰኚኝ!” ይሏታል፡፡ በወር ውስጥ የሆነ ፊልም ላይ ብቅ ትላለች፡፡ ‘ብቅ’ ማለቷን የምታውቁት እንዴት መሰላችሁ… ከእኛ ፀጉር ብዙም የማይበልጠው ፀጓሯ… አለ አይደል… “ወገቧ ላይ የተዘናፈለው ዞማ ፀጉሯ…” ምናምን አይነት ሆኖ ቁጭ፡፡ (በቀደም የሰማናት… “በተገዛ ፀጉር በተገዛ ቅንድብ…” የሚል ስንኝ ያለባት ግጥም በጣም ተመችታናለች፡፡)
እናላችሁ…አንዲት ፊልም ላይ ‘ብቅ’ በማለትና አንድ ነጠላ ዜማ በመልቀቅ ‘ሴሌብሪቲ’ የሚኮንባት የእኛዋ አዲስ ነገር መፍጠር የማይገዳት ይቺው ጦቢያችን ነች፡፡
በነገራችን ላይ ሰሞኑን የተለያዩ የቲቪ ጣቢያዎች ላይ ያየናቸው የመዝናኛ ዝግጅቶች አንዳንዶቹ ደህና ነበሩ፣ ምንም እንኳን ብዙም “ብራቮ!” የምንልባቸው የፈጠራ ነገሮች ባናይም፡፡ አንዳንዶቹ ዝግጅቶች ግን የበዓል ልዩ ዝግጅት መባላቸው…ጉድ ነሽ የአንኮበር ቅጠል አሰኝቶናል፡፡ አብዛኞቹ ዝግጅቶች ላይ ግን ይቺ የ‘ሴሌብሪቲ’ ባህል ውስጣችን ምን ያህል እየሰረጸች እነንደሆነ የሚያሳዩ ነገሮች ነበሩባቸው፡ አሀ…ዝግጅት አዘጋጆቹ እኮ ‘አርቲስቶቹን’...አለ አይደል…“ሲሻሟቸው ከርመው ነበር እንዴ!” የሚያሰኝ ነው፡፡ አርቲስቶቻችን…ሁሉም ላይ መታየት መሰላቸት እንዳያመጣ  አስቡበትማ! ልክ ነዋ!… በማስታወቂያዎቹ እንኳን አብዛኞቹ ፊቶች ‘የለመድናቸው’ እየሆኑብን ነው!)  
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ደግሞላችሁ ‘የወንበር ሱስ’ ያለባቸው አሉላችሁ፡፡ የምር…አይደለም ሦስት መንግሥት፣ አሥራ ሦስት መንግሥትም ቢለዋወጥ የሆነ ‘ወንበር’ ላይ አይጠፉም! እንደውም ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… እንዲህ አይነት ሰዎች ዓለምን ሲሰናበቱ ምን ብለው ሊናዘዙ ይችላሉ መሰላችሁ… “አደራ እንደሌላው ሰዉ ሳጥን ውስጥ እንዳትከቱኝ! የሆነ ወንበር ላይ አስቀምጣችሁ ቅበሩኝ…” ሊሉ ይችላሉ፡፡
እናላችሁ…እንዲህ አይነት ሰዎች አንድ ጊዜ የሆነ መሥሪያ ቤት አለቃ ይሆናሉ፣ ሌላ ጊዜ የሆነ የምናምን ኮሚቴ ሰብሳቢ ይሆናሉ፣ ሁሉም ቢጠፋ እንኳን እንደምንም ብለው የዕድር ዳኛ ይሆናሉ…ይህም ካልሆነ ደግሞ ጓደኞቻቸውን ሰብስበው ሰባት ሰው ያሉባት ዕቁብ ይመሠርቱና የዕቁብ ጸሀፊ ይሆናሉ፡፡
ከወንበር ሱስ ይሰውራችሁማ!
ደግሞላችሁ… እንዲሁ የሰማዩንም የምድሩንም ሁሉንም ነገር የማጣጣል፣ የመወንጀል ሱስ ያለባቸው አሉ፡፡ የምር…መድረክ ላይ ሲወጡ የሆነ ክፍልን ወይ ቡድንን ‘ወጋ’ ሳያደርጉ መውረድ አይፈልጉም፡፡ ልክ ነዋ…በየስብስባው “የራሳቸው ድብቅ ዓላማ ያላቸው…” አይጠፉማ! (እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እዚህ አገር… አለ አይደል… ስብሰባው ላይ የተገኙት ሁለት ሰዎች ብቻ ቢሆኑ እንኳን አንደኛው ‘የራሱ ድብቅ ዓላማ ያለው መሆኑን’ አትጠራጠሩ፡፡ እንደውም…ማመልከቻ የሚያስገባልን አጥተን ነው እንጂ…‘በነፍስ ወከፍ የድብቅ ዓላማ’ ብዛት ጊነስ ቡክ ውስጥ ባንገባ ነው!)
እናላችሁ…ሁሉንም የማጣጣል ሱስ ያለባቸው ሰዎች የሚሉት ቢያልቅባቸው እንኳን… እንደምንም ብለው “በዓጼ ልብነ ድንግል ዘመን ህዝቡ ኢንተርኔት እንዲጠቀም አይበረታታም ነበር…” ምናምን ከማለት ወደኋላ አይሉም፡፡
ከመወንጀል ሱስ ይሰውራችሁማ!
(ስሙኝማ…እግረ መንገዴን፣ ይሄ ‘ኒኦ ሊበራሊዝም’ የሚሉት ‘ጭራቅ’ ነገር…እንኳንም ‘ክላስሜቴ’ ምናምን አልሆነ! አሀ…ሰሞኑን ሲወርድበት እንደከረመው ውግዘት ለሌላውም መትረፉ አይቀርማ! ወይ ደግሞ…መቼም ‘ክላስሜት’ ስለነበር እናዝንና… “እንደው እንደዛ እንትን የነካው እንጨት ሲያደርጉት ሆዴን ቦጭ፣ ቦጭ አደረገው…” እንልና…‘ራዳር’ ውስጥ ልንገባ እንችላለና!)
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሆነ አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ…ዘንድሮ የባህል መድኃኒት አዋቂውም፣ ዘመናዊ ክሊኒኩም፣ ሆነ ኮከብ ቆጣሪውም ምናምኑም “...ስንፈተ እንትን ካለባችሁ ወደ እኛ ኑ…” እያሉን ነው፡፡ እኔ የምለው…ይሄን ያህል ደክመናል እንዴ! የተጠና ነገረ ካለ ይነገረና! አሀ…እኛ የምናየው ነገር ሁሉ… ‘ስንፈተ ምናምን…’ ሳይሆን…አለ አይደል…አሥራ ሦስቱም ወር የሀበሻ ልጆች ‘ሜቲንግ ሲዝን’ ምናምን የሆነ ነው የሚመስለዋ! ቂ…ቂ…ቂ…
ይልቅስ፣ ምን መሰላችሁ… አቅማችን ለደከመው ብቻ ሳይሆን ኸረ ለበዛብንም መፍትሄ ይፈለግልን! ልክ ነዋ… የእንትን ሱስ ያለብን መአት ነና! ልጄ…በቀን ስንት ጊዜ የሚያንደረድረን እኮ ብንሰባሰብ በህዝብ ቁጥር ከዓለም አራተኛ የሆነ ‘ኪንግደም’ መመስረት የምንችል ይመስላል፡፡ (ወዳጄ… ያ በቀን አምስት ጊዜ ምናምን የሚያሯሩጠው ሰውዬ… ቀለለለት ወይስ ጭራሽ ተቆለለበት! የእሱ እኮ የሚገርም ነው…እንኳንም የመርካቶ ነጋዴ ሆነ፡፡ የዓለም የነዳጅ ‘ኰስት’ እንኳን በየቀኑ ይሄን ያህል አይወነጨፍም! ቂ…ቂ…ቂ… በነገራችን ላይ የሚያሯሩጠው ሰውዬ ነገር ‘እውነተኛ ታሪክ’ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ “ሰው እንዲህ ይቀጠናል!” የሚለውን ጥያቄ የምትተዉት ‘ሱሱ’ን ስታውቁለት ነው፡፡)
እናማ ከንእትን ሱስ የሚያላቅቅ የባህልም ሆነ ዘመናዊ መፍትሄ ይፈለግልንማ!
ከእንትን ሱስ ይሰውራችሁማ!
ደግሞላችሁ…የ‘ቦተሊካ’ ሱሰ ያለብን አለን፡ እንክት! አሁንም እንደግመዋለን የ‘ቦተሊካ’ ሱስ ያለብን አለን፡፡ አለ አይደል…እንደ ነፋሱ አነፋፈስ የምንወዛወዝ፡፡ ከፍ ብለን እንዳልነው የሦስት መንግሥታት ዓይነ ውሀ ‘ተስማምቷቸው’ የሚኖሩ ‘ቦተሊከኞች አሉ፡፡ ይሄ እኮ እንዴት አይነት ከእንትኑ የተጣላ ‘ኦፖዚሽን’ ምናምን መሰለህ…“ሲባል የምንጠይቀው ጥያቄ “በዛ ሰሞን የዘመኑ ሰው ነው፣ ምናምን ስትሉ አልነበረም እንዴ!” ምናምን የሚል ነው፡፡ የ‘ቦተሊካ’ ጂምናስቲክ ዓለም አቀፍ ውድድር ይዘጋጅልን፡፡ እኔ የምለው… እኛ አሪፍ፣ አሪፍ በሆንንባቸው ነገሮች ውድድር የማይዘጋጅሳ! ልጄ በ‘ቦተሊካ አጥር ዘለላ’ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ማንም አይደርስብንም፡፡በእግር ኳስ እንኳን ከአንድ ክለብ ወደሌላ ለመዘዋወር ስንትና ስንት ጣጣ አለበት፡፡ በኛዋ ጦቢያ ‘ቦተሊካ’ ግን ከአንዱ ካምፕ ወደሌላ ካምፕ መዝለልን የመሰለ የሚያፈጥን ነገር ያለ አይመስልም፡፡ ደግሞላችሁ… ‘ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ’ ነገር የሚሆኑት እነኚህ የቦተሊካ አጥር ዘላዮች ናቸው፡፡ከ‘ቦተሊካ’ አጥር ዘለላ ሱስ ይሰውራችሁማ!
“በሱስ ብዛት የምዕተ ዓመቱ ግብ…” ምናምን የሚል ነገር ያለ እያስመሰለብን ነው፡፡
አንድዬ ከሱስ ሱናሚ ይጠብቀንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Page 13 of 15