አቶ ዮናስ ካሳሁን የተባለ ግለሰብ የወ/ሮ አኪኮ ስዩምን ኢ-ሜይል አድራሻ የይለፍ ቃል (ፓስወርድ) ያለ ግለሰቧ ፈቃድ ባልታወቀ መንገድ በመጠቀም ግለሰቧ ከተለያዩ ሰዎችና ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን የመረጃ ልውውጥ ወደራሱ አድራሻ በመላክ፣ በማጥፋትና ለ3ኛ ወገን አሳልፎ በመስጠት ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ፡፡ ግለሰቡ በአሁኑ ሰዓት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ፍ/ቤቱ ለሰኞ ጠዋት ቀጠሮ ይዟል፡፡
 የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆነችው የግል ተበዳይ ወ/ሮ አኪኮ ስዩምን የኤሌክትሮኒክ አድራሻ ባልታወቀ መንገድ አልፎ የግል የመረጃ ልውውጦቿን ወደራሱ አድራሻ መላኩና ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠቱ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መረጋገጡም ታውቋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከኤሌክትሮኒክስ አድራሻ (ኢ.ሜል) መረጃ የመስረቅና የማጥፋት ወንጀል ዙሪያ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርግለት በጠየቀው መሰረት፤ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ለመፈፀም በህገ-ወጥ መንገድ የተበዳይዋን የወ/ሮ አኪኮ ስዩምን የኤሌክትሮኒክ አድራሻና የይለፍ ቃል (ፓስወርድ) ባልታወቀ መንገድ በመጠቀም ግለሰቧ ከተለያዩ ሰዎች እና ድርጅቶች ጋር የምታደርገውን የመረጃ ልውውጥ ወደ ራሱ ከመላኩም በተጨማሪ ኢ/ር ግርማ ገላው ለተባለ ሶስተኛ ወገን መላኩን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያረጋገጠ ሲሆን ግለሰቧ በተለያዩ ወቅቶች ለተለያዩ የንግድ ስራዎች ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር መልእክት የተላላከችበትን ቀናት በአገራችንና በአውሮፓውያን ዘመን ቀመር በግልፅ አስቀምጦ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ልኳል፡
ከኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ሦስት ጠበቆች አንዱ የሆኑትን አቶ ወገኔ ካሳሁንን አነጋግረን በሰጡን ምላሽ፤ ተከሳሽና ተበዳይ ቀደም ሲል የፍቅር ግንኙነት እንደነበራቸውና ግንኙነታቸው መቋረጡን፣ ከዚያ በኋላ የተበዳይዋን የኢሜል ሳጥን በመስበር በርካታ መረጃዎችን እንደሰረቀ በመታወቁ መረጃዎቹን እንዲመልስላት ራሷም በአማላጅም ጠይቃው እንደነበር ጠበቃው ተናግረዋል፡፡
“ተጠርጣሪው መረጃዎቹን እንድመልስልሽ 40 ሚሊዮን ብር ክፈይኝ፤ ያለበለዚያ መረጃውን አልመልስም” ማለቱን የጠቆሙት ጠበቃው፤ ከዚያም ወመረጃዎችን በመያዝ ክስ መመስረቱን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
“ምስክሮች እንድናቀርብ ፍ/ቤቱ ጠየቀን፤ በምስክርነትም ራሷ ተበዳይና የሰረቃቸውን የኢ-ሜይል መረጃዎች እንዲመልስላት አማላጅነት የላከቻቸው ሰዎች ቀርበው የሚያውቁትን አስረዱ” ያሉት ጠበቃው፣ ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ ተጠርጣሪው በበቂ ሁኔታ መከላከል ባለመቻሉና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲም ሆነ ምስክሮች በበቂ ሁኔታ ጥፋተኝነቱን በማረጋገጣቸው ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤቱ ጥፋተኛ ብሎታል ብለዋል፡፡
ፍ/ቤቱ የቅጣት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ተጠርጣሪው ማረሚያ ቤት እንዲቆይ ያዘዘ ሲሆን የቅጣት ውሳኔውን ለመስጠት ለሰኞ ጠዋት 3፡30 ሰዓት ቀጠሮ ይዟል፡፡
“በአገራችን የግለሰቦችን የመረጃ ሳጥን በህገ-ወጥ መንገድ በመስበር ጥፋተኛ የተባለ ሰው ስሰማ የመጀመሪያዬ ነው” ያሉት የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ጠበቃ፤ እነዚህ ወንጀሎች በአገራችን አዲስ ናቸው፤ በ1949 የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ላይ አልተካተቱም፤ በአዲሱ ላይ ግን ተካተው ይሄው እየሰሩ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
 ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ በኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ በውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ በአስጐብኚ ድርጅትና ማሽነሪዎችን በማከራየት እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማራ ኩባንያ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ዜና

በአሁን ወቅት ሰላም ሰፍኗል ተብሏል በቴፒ ከተማ በተደረገው ውይይት ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ተገኝተዋል

     በጋምቤላ ክልል ባለፉት ሳምንታት ግጭት ተቀስቅሶባቸው በነበሩ አካባቢዎች በአሁኑ ሰዓት ሰላም ሰፍኗል የተባለ ሲሆን በግጭቱ ተሳትፈዋል የተባሉ አመራሮችንና ሌሎች አካላትን በቁጥጥር ስር አውሎ ወንጀለኛን የመለየት ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡ ሰሞኑን የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በተገኙበት ግጭቱ በተፈጠረባቸው የደቡብ ክልልና የጋምቤላ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች አመራሮችና ሌሎች የየክልሎቹ ከፍተኛ ባለስልጣናት የ3 ቀናት ውይይት በቴፒ ከተማ አካሂደዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የጋምቤላ ክልል የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳይመን ቱርያል ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት በተገኙበት በተካሄደው ውይይት በግጭቱ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ግጭቱ ተቀስቅሶባቸው የነበሩት የጎደሬ ወረዳና አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በአሁን ሰዓት መከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ጥበቃ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት ባለስልጣኑ፤ በአካባቢው ሰላም መስፈኑንም ተናግረዋል፡፡
የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠሩን ተከትሎም ህብረተሰቡ ወደ ቀዬው ተመልሶ ሰላማዊ ኑሮውን እየመራ ነው የተባለ ሲሆን ት/ቤቶችም መደበኛ የመማር ማስተማር ስራቸውን መቀጠላቸውም ታውቋል፡፡
በግጭቱ የጠፋው የሰው ህይወትና የወደመው ንብረት በመጣራት ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በግጭቱ ተሳታፊ መሆናቸው በተረጋገጠባቸው አካላት ላይ በሁለት ሳምንት ውስጥ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡
በአካባቢው ለሁለት ሳምንት በዘለቀው ግጭት የውጭ ሃይሎች ተሳታፊ ሳይሆኑ እንዳልቀረም በውይይቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አመት ዋዜማ ከተቀሰቀሰውና በጎደሬ ወረዳ መዘንገር ዞን ከተፈጠረው ግጭት በተጨማሪ በዚሁ ወረዳ ቴፒ አካባቢ በቅርቡ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች መንገድ ላይ አድፍጠው በመጠበቅ ከአስር በላይ የፌደራል ፖሊስ አባላትን ገድለዋል፡፡

Published in ዜና

          ኢህአዴግ ብዙ ይዘገያል እንጂ አንዳንድ ነገሮችን እኮ ይቀበላል፡፡ (ምንጩን አጣርቶ ነው ታዲያ!) ምን ሰምተህ ነው አትሉኝም! ሰሞኑን በEBC እንደሰማሁት፣ የመንግስት ተቋማት የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች (የህዝብ ግንኙነት ለማለት ነው) በፌስ ቡክ አጠቃቀም ላይ ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን ዓላማውም በማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ የሚሰራጩ “በሬ ወለደ” ዓይነት ውሸቶችን ለመመከትና እውነታውን ለማሳወቅ ነው ተብሏል፡፡ ደስ አይልም - ውሸትን በእውነት መመከት!! (እውነት አንፃራዊ ናት እንዳትሉኝ!) ለማንኛውም ግን ፌስ ቡክን እዘጋዋለሁ ከሚል ‹ቴረር› ወይም ‹ሆረር› ሺ ጊዜ ይሻላል (ይሻላል ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ውሳኔ ነው!) በነገራችሁ ላይ በግል ፕሬሶችም ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ይሻል ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ እኒያን ሁሉ የፕሬስ ውጤቶች ዝም ጭጭ ከማሰኘት ማለቴ ነው፡፡ (ያኔ አልተገለጠለት ይሆናላ!)
ወደ ሌላ አጀንዳ ከማለፋችን በፊት አንድ ሁለት ቀልዶችን ብነግራችሁስ፡፡ ሰውየው የአውራው ፓርቲ ወይም የ“ልማታዊ መንግስታችን” ካድሬ ነው - የቀልድ ምንጮቼ እንደነገሩኝ፡፡ እናላችሁ…የመንግስት ሃላፊዎች የሃብት ምዝገባ ሲካሄድ ይሄም ካድሬ ሃብቱን ሊያስመዘግብ ተገኝቶ ነበር (ካድሬም ለካ ሃብት አለው!) በምዝገባው ሂደት ላይ ታዲያ “የሥራ ዓይነት” ሲል ይጠይቃል፤ የሃብት መዝጋቢው - ካድሬውን፡፡ (“ካድሬነት” የሚል ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል!) ካድሬ ሆዬ፤ የሥራ ዓይነት ሲባል “መንግስትነት” ብሎ አረፈው፡፡ እዚህ አገር ለመጀመርያ ጊዜ ነው እንዲህ ያለ ሥራ መኖሩን የሰማሁት፡፡ እኔ እሱን ብሆን ግን “መንግስትነት” ሳይሆን “ኢህአዴግነት” ነበር የምለው፡፡ እውነት ግን ለካድሬ የሚቀርበው የትኛው ነው? መንግስት ወይስ ኢህአዴግ? ቀልዱ ያን ያህል ፍርፍር አድርጐ ባያስቅም በኢህአዴግ ካድሬዎች ላይ ጥናት ለሚያካሂዱ የፖለቲካ ምሁራን ጥሩ ግብዓት እንደሚሆን ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡
ሌላ ቀልድ ልጨምርላችሁ፡፡ ይሄኛው መራራ ቀልድ (bitter humour) የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ (“መራራ ኑሮ ላይ መራራ ቀልድ” እንዳትሉኝ!) ቀልዱን አንድ ጉምቱ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፤ የኢህአዴግ ከፍተኛ ሹማምንት በተገኙበት መድረክ ላይ የተናገሩት እንደሆነ ስለሰማሁ ዘና ብላችሁ አንብቡት (ቀልድ እኮ የህዝብ ሀብት ነው!) ከህአዴግ ጋር ከምር የምጣላው መቼ መሰላችሁ? ቀልድ እንደ መሬት ሁሉ የህዝብና የመንግስት ሃብት ነው ያለ ጊዜ! (ቀልድ በሊዝ በጄ አንልማ!)
ወደ ቀልዱ እንሂድ፡፡ ኢህአዴግና ሰይጣን፤ ቤት ለመከራየት አንዲት በእድሜ የገፉ ባልቴት መኖሪያ ቤት ይሄዳሉ፡፡ ሁለቱም እኩል ስለደረሱ የኪራዩ ዋጋ ጨረታ ዓይነት ነገር ሆነ፡፡ ኢህአዴግ ጨረታውን በአሸናፊነት ለመወጣት ቆርጦ ስለተነሳ፣ ከተጠየቀው የኪራይ ዋጋ ከፍ አድርጐ ተናገረ፡፡ (ሰይጣንን ወደመጣበት ለመመለስ!) አሮጊቷ የሁለቱንም እጩ ተከራዮች ሃሳብና አቅም ለአፍታ ያህል ከገመገሙ በኋላ ቤታቸውን ለሰይጣን እንደሚያከራዩት ይፋ አደረጉ፡፡ (በሙስና መሆን አለበት!) ኢህአዴግ ክው አለ (ከ97 ምርጫ በኋላ “ከፍተኛው ድንጋጤ” በሉት!) ለመረጋጋት እየሞከረ፤ “ምነው እናት፤ እኛ ከፍ ያለ ገንዘብ አቅርበናል፤ በዚያ ላይ ከ20 ዓመት በላይ ህዝባዊነታችንን በተግባር አረጋግጠናል፡፡ እንዴት እኛን ትተው ለዚህ ለከሃዲ ሰይጣን ያከራያሉ?” ሲል ጠየቀ፤ ኢህአዴግ፤ በቁጣና በመማፀን መሃል እየዋለለ፡፡ እሳቸውም “ሰይጣን እኮ ቢያንስ በፀበል ይለቃል…” አሉ፡፡ (“ኪራይ ሰብሳቢ” ብዬ ልፈርጃቸው አልኩና የዕድሜ ባለፀግነታቸው አሳሳኝ!)
ዘመኑ በከፊልም ቢሆን ነፃ ገበያ ነውና ኢህአዴግ አሮጊቷን “የኒዮሊበራል ቅጥረኛ” ብሎ ከመፈረጅ ውጪ ሌላ ምንም ማድረግ አልቻለም (ይሄ የእኔ ግምት ነው!) እኔ የምለው የሸማቾች ማህበር የሚባለው ተቋም፤ የግል ቤቶችን የኪራይ ተመን ሊያወጣ ነው የሚባለው ከምር ነው እንዴ? (“ነፃ ገበያ” መንምና መንምና “ገበያ” ብቻዋን ልትቀር ነው!) በነገራችሁ ላይ ይህቺን ቀልድ የፈጠሯት ሥልጣን ይገባናል ባይ ወገኖች ሳይሆኑ አይቀርም (ጥርጣሬ ነው!)፡፡ ግን እኮ ሥልጣን በምርጫ እንጂ በፀበል አይገኝም፡፡  
በቅርቡ ኢትዮጵያና ማሊ እዚህ አዲስ አበባ ስታዲየም ተጋጥመው በተሸነፍንበት ወቅት ኢህአዴግ “የሻዕቢያ ቅጥረኞች” እንደሚላቸው ዓይነቶቹ የሚሊን ቡድን “ኢቦላ! ኢቦላ!” በማለት ለማብሸቅ ሞክረው ነበር አሉ፡፡ (እብደት እኮ ነው!) የሆኖ ሆኖ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተራው ማሊ ሄደና ድል ቀናው፡፡
አሸነፈ፡፡ ድል ብቻ ግን አይደለም፡፡ ፈተናም ገጥሞት ነበር አሉ፡፡ (ከዚህ ይጀምራል ቀልዱ!) እናም ቂም በሆዳቸው የቋጠሩት ማሊዎች ሰብሰብ ብለው “አገራችሁ የመጣን ጊዜ ለምንድነው ‹ኢቦላ! ኢቦላ!› እያላችሁ የሰደባችሁን? ሲሉ አፋጠጧቸው፡፡ የቡድናችን ተወካዮችም “መሳደባችን እኮ አይደለም…እኛ አገር ‹ኤቦ…ኤቦ ላላ›” የሚል ዘፈን ስላለ ነው” በማለት በብልሃት ተወጡት፡፡  
አንዳንዴ የሚቀለድበትና የማይቀለድበትን ነገር መለየት ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ እውነቱን ልንገራችሁ አይደል … “ኢቦላ” ብሎ መሳደብ ኋላቀርነትም ኢ-ሰብዓዊነትም ነው፡፡ (እልም ያለ ፋርነት በሉት!)
ባለፈው ሳምንት ደግሞ የአሜሪካ ኤምባሲ ቦሌ ኤርፖርት አካባቢ አልሸባብ ጥቃት እንደሚሰነዝር መረጃ ደርሶኛልና ዜጐቼ ጥንቃቄ አድርጉ የሚል መልዕክት ማስተላለፉን ተከትሎ፣ በፌስ ቡክ ላይ “መንግስት 1፣ አልሻባብ 0” የሚል ፌዝ ወጥቶ ነበር፡፡ ሰው በራሱ ህይወት ያፌዛል እንዴ? ሽብር ማለት እኮ ሌላ ሳይሆን ቦንብ … ፈንጂ … እልቂት … ግድያ ጥፋት … ማለት ብቻ ነው፡፡ ሽብርተኞች ማለት ደሞ … እነ አልቃይዳ፣ እና አልሻባብ፣ እነ ቦካሃራም፣ እነ አይሲስ… አይነቶቹ ናቸው፡፡ (እነሱ እኮ ፌዝ አያውቁም!)
እኔ የምለው … ባለፈው ሳምንት የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ኢቦላ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመግባቱን ለህዝቡ ለማረጋገጥ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ላይ “ሻዕቢያ ያሰራጨው ወሬ ነው” ሲል የሰማሁ መስሎኛል፡፡ አይገርማችሁም… ሻዕቢያ ሌላው ሲያቅተው “የኢቦላ ሽብር” መንዛት ጀመረ ማለት ነው (እውነትም ተስፋ ቆርጧል!)
ወጋችንን እንግዲህ በቀልድ እንቋጨው፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ ይሄኛውም ከመራራ ቀልዶች (bitter humor) የሚመደብ ነው፡፡ አይገርማችሁም … በዚህ ሳምንት ከሶስት ሰዎች የደረሱኝ ሶስቱም ቀልዶች ምርር ያሉ ናቸው፡፡ (መራራ ቀልድ የመራራ ኑሮ ውጤት ነው ልበል?) እናላችሁ አንድ ከፍተኛ የህንድ ባለስልጣን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ይመጣሉ፡፡ ጉብኝቱ የተጀመረው የቻይና የእጅ ሥራ ውጤት ከሆነው ከቀለበት መንገድ ነው አሉ፡፡ ከዚያም በጎተራ ማሰላጫ አድርገው… በቅዱስ ዮሴፍ ቤ/ክርስትያን በኩል ያልፋሉ፡፡ የህንዱ ባለስልጣን በርካታ ሃውልቶች ያዩና ጥያቄ ያቀርባሉ፤ “ይሄ ደሞ ምንድነው?”
የገዢው ፓርቲ የመንግሥት ተወካይ፤ “የሞቱ ዜጎቻችን የሚያርፉበት ሥፍራ ነው”
የህንድ ባለስልጣን፤ “እነዚህ ሁሉ … ለምን እንደኛ አታቃጥሏቸውም?” (በህንድ አስከሬን የማቃጠል ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዳለ ልብ ይሏል!)
የመንግስት ተወካይ፤ “አይ … እኛ በቁማቸው ነው የምናቃጥላቸው”
በነገራችሁ ላይ የዚህ ቀልድ ባለቤት ህዝብ ነው! (ኮፒራይቱም የህዝቡ ነው ማለት ነው!)

ውድ ፕሬዚዳንት ኦባማ፡-
ጠብመንጃን መጠቀም ማቆም እንችላለን? እባክህ ማንም ሰው ጠብመንጃ የምትችለውን ሁሉ እያደረግህ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በጣን ነው የማመሰግንህ፡፡
ታጃህ - የ10 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ኦባማ፡-
ጠብመንጃን በተመለከተ አንዳንድ የህግ ለውጦች መደረግ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ አሜሪካ ነፃ አገር ናት፤ ቢሆንም ግን በጠብመንጃ ላይ ገደብ መደረግ አለበት የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ እባክህን ሰዎች ከባድ መሳሪያ እንዲይዙ አትፍቀድላቸው፡፡ መሳሪያ ለመያዝ በቂ ምክንያት ሊኖር ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ባለፈው ጊዜ ት/ቤት ውስጥ በተከሰተው ግድያ በጣም አዝኛለሁ፡፡
ጆሲ - የ12 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ኦባማ፡-
እኔ የምኖረው ቺካጐ ውስጥ ነው፡፡ 9 ዓመቴ ነው፡፡ ያንተም ሴት ልጅ 9 ዓመቷ ይመስለኛል፡፡ አዲሱ ቤትህን እንደወደድከው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አሁን በጣም ዝነኛ ሆነሃል፡፡ አዲሱ ቤትህ ፒዛ ልትጋብዘኝ ትችላለህ? ኦባማ፤ ይመችህ!
ብሪያን - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ካርተር፡-
እባክህን ሰዎች ዓሳ ነባሪዎችን እንዳይገድሉ አስቁማቸው፡፡ በየወሩ ብዙ ዓሳ ነባሪዎች እንደሚገደሉ አውቃለሁ፡፡ ለእነሱ ጥበቃ የሚያደርግ ህግ ብታወጣም ጥሩ ይመስለኛል፡፡
ቦቢ - የ12 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ካርተር፡-
በጣም ግሩም ሰው ትመስለኛለህ፡፡ ኦሃዮን ከገባችበት የኢነርጂ (ሃይል) ቀውስ በማውጣት አሜሪካን መለወጥ ያስፈልጋል ያልከው ነገር ትክክል ይመስለኛል፡፡ ገና 13 ዓመቴ ቢሆንም እንደ አሜሪካ ፕሬዚዳንትነትህ በጣም እወድሃለሁ፡፡
ብሪያን - የ13 ዓመት ህፃን

Published in ጥበብ
Monday, 20 October 2014 08:40

እንቆቅልሽ

  • ከአንድ ፓውንድ ላባና ከአንድ ፓውንድ ሸክላ የትኛው የበለጠ ይመዝናል?
    • በግድግዳ ውስጥ መመልከት እንድንችል ያደረገን የፈጠራ ውጤት ምንድን ነው?
    • በጨለማ ክፍል ውስጥ ነኝ ብለህ አስብ፡፡ እንዴት ከጨለማ ክፍሉ ትወጣለህ?
    • ቆዳዬን ስትገፉኝ እኔ ሳላለቅስ እናንተ ታለቅሳላችሁ፡፡
    • ስትመግቡኝ እኖራለሁ፤ ውሃ ስታጠጡኝ ግን እሞታለሁ፡፡

 


    መልስ
ሁለቱም እኩል ናቸው
መስኮት
ማሰቡን በማቆም
ሽንኩርት
እሳት


Published in ጥበብ
Monday, 20 October 2014 08:38

ማራኪ አንቀፅ

    ማታ ከራት በኋላ መኝታ ክፍሌ ውስጥ ብቻዬን ነበርኩ፡፡ በሩ ተንኳኳና ከፈትኩት፡፡ ጋናዊቷ ሄለንና ሲዳናዊቷ አህላም ቆመዋል፡፡ ተዘግቶ ከነበረው በር በስተጀርባ እንደ እኔ ለሥልጠና የመጡ ሴቶች ቆመው አያለሁ የሚል ደቃቅ ግምት እንኳን ስላልነበረኝ ግራ ተጋባሁ፡፡ እኔ ዩኒቨርሲቲ ስማር ሴቶች ወደ ወንዶች፤ ወንዶችም ወደ ሴቶች መኝታ ክፍል ድርሽ እንዲሉ አይፈቀድም ነበር፡፡ ግር ቢለኝም ቀድሜ፣ “ታዲያስ! እንዴት ናችሁ?” ያልኳቸው እኔ ነበርኩ፡፡ ፊቴ ግን፣ “ምነው በሰላም ነው ወደ ወንዶች ዶርም የመጣችሁት?” የሚል ጥያቄ ከአንደበቴ በላይ ጮኸ እንደጠየቃቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡
ምናልባት በቃል ካቀረብኩት ሰላምታ ይልቅ ፊቴ ላይ የተንፀባረቀው ጥያቄ በጉልህ ተሰምቷት ይሆናል፤ ጋናዊቷ ሄለን ለሰላምታዬ ምላሽ ሳትሰጥ፣ “አህላም አብረኸን ወደ ባሩ እንድንሄድ ትፈልጋለች፡፡” አለችኝ ፈገግ ብላ፡፡ ከእንግሊዝኛዋ ከምዕራብ አፍሪካ ከመጡ ሰልጣኞች ጋር ጭራሽ የማይነፃፀር ጥርት ብሎ የሚሰማ ነው፡፡ ዩጋንዳ የገባሁት ከሁለት ቀናት በፊት ነበር፡፡ እዚህ በምዕራብ ዩጋንዳ፣ ኪባሌ ደን ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ወደሚገኘው የማካራሬ ዩኒቨርሲቲ የመስክ ሥልጠና ጣቢያ ከሌሎች ሃያ ስድስት ሠልጣኞች ጋር የደረስነው ትላንት ነው፡፡
“አህላም ራሷ አትናገርም እንዴ ሄለን የምታወራላት?” ብዬ እያሰብኩ ዞር ብዬ በትዝብት ሳያት፣ ሱዳናዊቷ አህላም፣ “አዎ፣ ከእኛ ጋር እንድትመጣ ፈልገን ነበር፡፡” ብላ ቀይ ፊቷን በውብ ፈገግታ አደመቀችው፡፡ ፊቷ ላይ የዋህነትና ግልጽነት ይነበባል፡፡ ረጅምና ደርባባ ናት፡፡
መኝታ ክፍሌ ተንኳክቶ በሴቶች ስጋበዝ ከኩራት ይልቅ የተሰማኝ መደነቅ ነበር፡፡ የእኛ አገር ሴቶች መቼም እንዲህ አያደርጉም፡፡ ሱዳኖች እንዲህ ያደርጋሉ ማለት ነው? … አልመሰለኝም፡፡ አህላም የተለየች መሆን አለባት፡፡ ወይም ከእኔ ጋር ማምሸት እንደምትፈልግ ስትነግራት ሄለን አደፋፍራት ይሆናል ወደ መኝታ ክፍሌ የመጡት፡፡ … ለነገሩ ከሌሎች አፍሪካውያን ይልቅ እኔ ከሷ ጋር የሚቀራረብ መልክ አለኝ፡፡ ገና ካሁኑ ዘመዶቿን ናፈቀች ማለት ነው? ብዬ እያሰብኩ፣ ሰለቀኑ ውሏቸው እየጠየቅኳቸው ወደ ባሩ ስንወርድ አህላም ቁጥብ ለመሆን ሞከረች፡፡ እንግሊዝኛዋ ጥሩ ፍሰት የለውም እንጂ ለመግባቢያ በቂ ነው፡፡ ባሩ በረንዳ ላይ ተቀምጠን ለስላሳ ጠጣን፤ ዳማ ተጫወትን፡፡ አህላም ወሬ ለመፍጠር አልሞከረችም፡፡ ጭምት ሆነችብኝ፡፡ አንደበቷን ገና በእንግሊዝኛ ስላላፍታታችም የፈለገችውን እንደልብ ለማውራት ይቸግራታል፡፡ ከሷ ይልቅ በጣም ጥሩ እንግሊዝኛ ከምታወራው ከሄለን ጋር ብዙ ሳናወራ አልቀረንም፡፡ ከሷ ጋር ብዙ ባንጫወትም አህላም አጠገቧ በመቀመጤ ደስተኛ ነበረች፡፡
(ከደራሲ ኢዮብ ጌታሁን “አለላ መልኮች” የተሰኘ ልብወለድ የተቀነጨበ)

Published in ማራኪ አንቀፅ

ከኤፍሬም ሥዩም ዉርስ ትርጉም
የግዕዝ ጉባኤ ቅኔን እንደ ማንበብ

‘ተዋናይ’ በጐጃም የነበረ ፈላስፋ፣ ታላቅ ሊቅ፣ ቅኔን የፈጠረ ባህረ ምስጢሩን ዋኝቶ የመረመረ መሆኑን ተነግሮለታል:: ስሙ ለመጽሐፍ ርዕስ መሾሙ አግባብ ነዉ። ተዋነይ (ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና) 83 ግጥሞች ከግዕዝ ወደ አማርኛ ዳግም የተተቀኘባቸዉ፥ ዘመነኛ ተደራሲያን እንደገና ከግዕዝ ስንቅ ለመቋደስና በእሳቦቱም ለመደመም የፈቀደ ድንቅ መጽሐፍ ነዉ። ኤፍሬም ሥዩም ለስድስት አመት ያክል የግሉን ፈጠራ እየተቀኘ በተጨማሪም ከግዕዝ የሚተረጉመዉን ለመምረጥ ብዙ ዳክሯል፤ በዉርስ ትርጉም ግዕዙን በአማርኛ ዳግም ለማንጠር አልሰሰተም። ሻማ ቡክስም በሚመጥነዉ ጥራትና ዉበት አሳትሞ ለሀገር ቅርስ አብቅቶታል። ዛሬ በየስርቻዉ በተራ ወረቀት በድብቅ ሌላዉ አሳትሞት ሲነግድበት ለሱ ወይም ለነሱ ሳሙና ሰርቆ እንደ መቸርቸር ርካሽነት ቢመስልም፥ ለባለቅኔዉ ሆነ ለኢትዮጵያ ሥነጽሁፍ ለሚስገበገብ ይሰቀጥጣል፤ ይጐዳል፤ ወንጀልም ክህደትም ነዉ። “ጥበብ ለምን አንገቱን ይድፋ?”ብሎ ለመጠየቅ ብቻዬን ሰልፍ መዉጣት ባልችልም፥ ቢያንስ ቢያንስ ኤፍሬም ሥዩምን <ሀቅህ ያብጠረጥራል> ለማለት አንድ የግዕዝ ጉባኤ ቃናን ለማንበብ ደፍሬያለሁ። ይህ መጽሐፍ በሚመጥነዉ ኮስታራ ግምገማ ለመደመም የግድ ግዕዝን እንደ ቋንቋ መቻልን፥ ግጥሞቹ የተፍታቱበትም የተወሳሰቡበትም ዳራና ዐዉድ ማጤንን ይሻል። ጉባኤ ዘርግተዉ ቅኔና ትርጓሜ መጻሕፍትን ሲያስተምሩ ግዕዝ በአመዛኙ ሃይማኖታዊ ለሆነ ጉዳይ አድሯል። ቢሆንም አልፎ አልፎ የእለት ህይወትን፥ ለኑሮ መብሰልሰልን፥ ፈጣሪ መሞገትን፥ በሄዋን ገላ መጐምጀትን ... ከመሰለ ሰመመን መቅዘፉ መች ቀረ ? ከ83 ግጥሞች አንዱን ያዉም በአማርኛ መንቶ፥ በግዕዝ ጉባኤ ቃና የተባለዉን ባለ ሁለት ስንኝ ደፍርኩ እንጂ የተቀሩት ሰማንያ ሁለቱ ያመቁትን፥ እዉስጣቸዉ ያደባዉን ለማባበል አቅም ይጠይቃል።

ድንግል ወለት ትመስለነ ዕቤርተ
አኮኑ ትዉዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ

 [ከተዋነይገፅ 152 (65ኛዉ ግጥም)የተወሰደ።]
መምህር ይኄይስ ወርቄ <ንባብ ወትርጓሜ ዘቅኔያት- አዕማደ ምሥጢራት>በሚል መጽሐፋቸዉ ገፅ 29 ቃል በቃል ተርጉመዉታል። የተቀኙትም ዘዋሽራ ተክሌ መሆናቸዉን ይገልጣሉ።
ድንግል ልጃገረድ ባልቴትን ትመስለናለች፤
እሳትን አቅፋ ትዉላለችና
በዕድሜ መፍካትና መክሰም ጠቢባን ሲብሰለሰሉበት ከተባዕት ይልቅ ለእንስት ገላና ዉበት ይነዝራሉ። እንዳለጌታ ከበደ በ’ዛጐል’ ልቦለዱ እንደ መለመላት አብይ ገፀባህርይ እሌኒ የመሰለች። ‘ወንድ . . . መቋጫዉ የረዘመ አረፍተ ነገር ነዉ:: ራሱን የሚያሰለች፣ የሚጠና:: ሴት ግን ትወሳሰብ ይሆናል፣ ቅኔ ትሆን ይሆናል፣ ... ቁጥብነቷ ይማርካል፣ ... ምን እንደሆነ የማይታወቅ ስሜት መጫር የምትችል!’ እስከ ማለት የበቃች ናት:: መምህር ዘዋሽራ ተክሌ ለመፈላሰፍ የሄዋንን ገላና እድሜ መቀንበባቸዉ አይደንቅም፤ እራሱ ኤፍሬም ሥዩም በዚህም ይደመማል። ‘ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር’ገፅ 34
የበአሉ ለታ
ሲበተን ያየነዉ አረንጓዴዉ ሁሉ
በበአሉ ማግስት
ሲጠረግ ያየነዉ ግራጫዉ ሳር ሁሉ
ያንቺን ወጣትነት ይወክላል አሉ።
ከድንግል ልጃገረድ እስከ ባልቴት የተዘረጋዉ ሆነ የተጠቀለለዉን እድሜ ዉስጣዊ ፍምና የምድጃ ዳር ትካዜን በሁለት ስንኝ የግዕዙ ቅኔ ሲቋጥረዉ ይፈትናል። ይህ እምቅና አሻሚ ግጥም ነዉ። [ambiguity አሻሚነት ይላል ብርሃኑ ገበየሁ “ከአንድ ፍቺ በላይ ትርጓሜ መያዝ፥ ከግጥሙ ዐዉደ ንባብ በመነሳት ቁርጥ ያለ ትርጓሜ ለመስጠት አለመቻል። ‘የአማርኛ ሥነግጥም ገፅ 411’] “አሞኛል ስላቸዉ በሽታዬን አጡት/ የላጡት ይደርቃል እንኳን የቆረጡት” የመሰለ ቃል-ግጥም ደግሞ አሻሚነትን ይበልጥ ያስረዳ ይሆናል። ኤፍሬም የግዕዙን ግጥም በአማርኛ ሲወርሰዉ ይህን አሻሚነቱን ሳይፍቅ ሳያደበዝዝ ጠብቆታል።
የዐሥራ አምስት ዓመቷ
ያቺ ልጅ እግር ድንግል፥
ዘመኗ የሄደ
ዕድሜዋ የገፋን ባልቴት ትመስላለች
ምክንያቱም ...
እሳት በጉያዋ
ታቅፋ መኖርን ወዳለች። [ተዋነይ፥ ገፅ 153]

ልጃገረድና ባልቴት፥ ለአቅመ ሄዋን የደረሰች እና ያረጀች ያፈጀች አሮጊት ሁለቱም የሚያቅፉት እሳት ለየቅል ነዉ።  በእድሜ ጠና ያሉት ከኑሮ ልምድና ተመክሮ የሰበሰቡት ማለፊያቸዉ ላይ ይበጃቸዉ ይሆን? ሎሬት ፀጋዬ በአፍላ ዕድሜዉ ስለ አንዲት አዛዉንት ያጤነዉ ያስደምማል። “ባንተያይ ባንወያይ፥ እቴቴ ዱብራ ኦሮሞ/ እንደልጅነት ሰመመን፥ ለካስ ዕድሜም ያማል ከርሞ።” ዘዋሽራ ተክሌ ዛሬ ፈክቶ ስለሚፋጅ ግን ከርሞ ስለሚያም ዕድሜ ነዉ የተቀኙት? ዓለማየሁ ገላጋይ በ’ኩርቢት’ ስብስቡ የቀረፃቸዉ ወደ እርጅና ጉዞ የጀመሩት ‘የቦኖ እናት’ ይታወሳሉ። “-ኧረ እኔስ ጨነቀኝ- አሉ የቦኖ እናት አፋቸዉን በአዳፋ ጨርቅ ሸፍነዉ። እታለማሁ መሀን በመሆናቸዉና ለሰፈርተኛዉ የቦኖ ዉኃ በማስቀዳታቸዉ ነው ‘የቦኖ እናት’ የሚል ቅጥል ስም የወጣላቸዉ። እታለማሁ በቅጽል ስማቸዉ አይከፉም። እንደዉም አንዳንዴ -እኔ የቦኖ እናት- እያሉ በራሳቸዉ ያሾፋሉ። ”የማኅበረሰቡ ሽኩሹክታ ገድበዉ ለመኖር ያልታከቱት ወደፊት ያለጧሪ ምድጃ ዳር ሲቆዝሙ ሊያሳስብ ይችላል። ልጃገረዷ እዉስጧ ፍትወታዊ ፍም ታቅፋ መፈልቀቅን ስታልም ባልቴትም መደበት ብቻ ሳይሆን በትዝታም እንደ መጋል እንደ መሎከስም ይዳዳቸዋል። “ትዝታ (ወደ ኋላ መፍሰስ) ትላንትን ዛሬ ላይ ከመመኘት የሚመጣ ነገር ነዉ። ዛሬ ላይ አብረዉን ያሉትን ሰዎች ወደ ኋላ አናስባቸዉም። ትናንት የተዉንን (የተዉናቸዉን) ሰዎች ግን ዛሬ ላይ ልናስባቸዉና ልንመኛቸዉ...ወደ ኋላ እንፈሳለን ከወንዙ ወደ ምንጩ”  ብሏል ኤፍሬም ሥዩም። [ፍቅር እዚህ ...] ለዚህም ነዉ ዘዋሽራ “አኮኑ ትዉዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ” ሲሉ አሻሚነቱ፤ እንደ መቆዘምም፥ በአለፈዉም ትዝታን ጐንጉኖ እንደ መፍካትም የተወሳሰበዉ። አዳም ረታ ‘በር’ በሚለዉ ትረካዉ የመለመላቸዉ ባልቴት የዕድሜ ቅዝቃዜ ብቻ ሳይሆን በትዝታም ግለት መሞቅና መቆጨትን ቋጥረዋል።
“ከሰዉ ሰዉ ደሞ ትዝ የሚላቸዉ፥ ኩታዉን እያመቻቸ መቶክቶክ የሚወደዉ ያ ብስል ቀይ፥ ነፍሱን ይማረዉና ነጭ ለባሽ ሆኖ ዉጋዴን ወድቆ የቀረዉ የአልጣሽ ልጅ፥ የሰፈር ወሬ ሲያቀብላቸዉ ነዉ። ከትዳራቸዉ ዉጭ የወደዱት ወንድ እሱ ብቻ ነበር። ግን ምንም አላደረጉም። ዛሬ ከሚቆጫቸዉ አንዱ የባቱን ጥንካሬ፥ ቁመቱንና አጨዋወቱን ያስታዉሱና ‘ቢሆን ኖሮ ማን ይጐዳ ነበር?’ ለራሳቸዉ ይላሉ። ለራሳቸዉ ይስቃሉ።” [ይወስዳል መንገድ ... ገፅ 228]
ከትዳር ቀለበት ሾልከዉ ሌላዉንም በወሲብ መቅመስ ሳይደፍሩ የቀሩት፥ በስተርጅና ለመቆጨትም በትዝታም ለመፍለቅለቅ እንደ ስንቅ ነዉ፤ ዕድሜ መች መክሰም ብቻ ሆነ? ዘዋሽራ ተክሌ ከነገረ መለኮት ሱባኤ ስሜታቸዉን ጐትተዉ ግራ ቀኝ ገላምጠዉ ድንግል ልጃገረድ ያቀፈችዉ እሳት እንዴት አባበላቸዉ? እንዴት ለመቀኘት እርሾ ሆናቸዉ? ቢያሰኝም በሄዋን ዉበት እና እጣ ፈንታ መመሰጥ ለባለቅኔ አንድ የህይወት ሰበዝ ነዉ። ጠና ያለ ምሁር ለአቅመ አዳም ባልደረሰች አጐጥጐጤ በፍትወት ፍላጐት ሲቅበዘበዝ እና ጣጣ ዉስጥ ሲወራጭ ዕዉቁ ደራሲ Nabokov በአብይ ልቦለድ አወሳስቦታል። Lolita በታተመ ወቅት ባህላዊና ሥነፅሁፋዊ ሽብር ለቆ ነበር። ዘዋሽራ የተቀኘላት ልጃገረድ የታቀፈችዉን እሳት ከሰብለወንጌል ጀምሮ በአያሌ ልቦለድ ተቀርፃለች፤ እንደ አዳም ረታ ግን በዝርግ ግጥም እስኪያደናግዝ ድረስ የተቀኘላት የለም። እንድያዉም የታቀፈችዉ ስሜታዊ እሳት ሲጥምም ሲጐመዝዝም የተተረከበት ‘የመጨረሻዋ የቀበሌ 01 ድንግል’ ልቦለድ አለዉ። ግን ‘ወተት’ የሚለዉ ትረካዉ ይበልጠ ዘዋሽራ “አኮኑ ትዉዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ” ላሉት ይመጥነዋል።
“እሁድ ከሰዓት በኋላ ነዉ፤ ጓደኛዬ ዳንኤል ቤት ስደርስ እህቱ የትምወርቅ ቧንቧ ስር ፀጉሯን ስትታጠብ አገኘሁዋት። ጡቶቿንም ። ከዚያንም ዕለት ጀምሮ ደህና እንቅልፍ አልወሰደኝም። ... ከቤት ስትወጣ ... አንድ ቄስ አቁመዉ ደረቷን ባረኩት።
‘ምን ብለዉ ባረኩሽ’ ስላት
‘እ እ እ’ ትላለች
‘እንዳይፈነዳ እሱዉ ይጠብቅልን?’
ጐኔን ቆነጠጠችኝ። እንደ ከረሜላ የሚጣፍጥ። መፈንዳቱ ይቀራል?... እጄን ትከሻዋ ላይ ጣል አደረክኩ ... በአንገቷ በኩል ወደታች አየሁ። የጡቶቿ መካፈያ(ሀ)ይመስላል፤ መልካም የተወለወለ ሀ ግዕዝ። ወይም የሚበር አሞራ። [ይወስዳል መንገድ ... ገፅ 210/218]
እንዲህ ከልጃገረድ አካል ከመሸገ ዉበት እንዲሁም ከባልቴት ባዶነት ሆነ ትዝታ ከተደበቀ ፍም ተላቀን ቅኔዉ ያጓተዉን የጊዜን ጥያቄ ብንነካካዉ በሰፊዉ ሊያወያይ ይችላል። ጊዜ እነ እትዬ አልታዬን “... በስዉር እጁ ይዞ በጭካኔ ሳይሆን እየሳቀ በዝግታ እንደ ወረቀት ጭርምትምት ...” ሲያደርጋቸዉ ስብሀት ተርኳል። እንደ አሜሪካዊ ደራሲ Faulkner አባባል፤ ጠቅላላ ችግሮቻችንን ማሸነፍ ብንችል ጊዜ ብቸኛዉ ችግራችን ሆኖ ይቀራል። የልጃገረዷ የየዋህነት ጊዜ፥ ባልቴቷም ላይ የተከማቸዉ ወቅት ለዘዋሽራ ተክሌ ሁለት አይነት እሳት -ብርሃንም ጨለማም- ይሆናል። የወጣት ገጣሚ ትዕግሥት ወራሽ ጥያቄ ያሳስበኛል።
ለምን ነበር?
መንጋትህ ላይቀር
ጨልመህ የነገስከዉ
መቅለልህ ላይቀር
እንደዚያ የከበድከዉ
ለምን ነበር ሌቱ
ቀንን የፈተንከዉ? [ነጭ ልብ  ከሚለዉ የግጥሞቿ ስብስብ የተወሰደ]
ጊዜ ጊዜን ሲፈትነዉ በቀንና ሌሊት ተምሳሌነት ገጣሚዋ መቅለሉንም መክበዱንም ስትጠይቅበት ዘዋሽራ ተክሌ ከልጃገረድ እስክ ባልቴት የተዘረጋዉን እድሜ ነዉ የተደመሙበት። Yevgeny ‘the Sole Survivor’ በሚለዉ መጽሐፉ “A poet’s autobiography is his poetry. Anything else is just a footnote” ያለዉ ያጠራጥራል። “የአንድ ባለቅኔ ግለህይወት፥ ታሪኩ ግጥሞቹ ናቸዉ፤ ሌላዉ ሌላዉማ የግርጌ ማስታወሻዉ ነዉ ”በግዕዝ የተቀኙት ግለታሪካቸዉ ከቤት ክህነት የተዋሀደ ቢሆንም እንደ ሰዉ የግርጌ ማስታወሻ አላቸዉ -የተሸሸገ። ይህን ለማግኘት መዳከር ኤፍሬም ሥዩም ቢሳካለትም የሐያሲያን ዝምታ ይገድበዋል። አንድ ባለ ሁለት ስንኝ ግጥሙ እንዲህ ከረቀቀብን ከ[ተዋነይ] መጽሐፉ የሚነዝሩት ሌሎች 82 ግጥሞች በምስጢራቸዉ ይማጠኑናል።
ጭራሽ በተራ ወረቀት እና ጥራት በሌለዉ ህትመት መጽሐፉ መዘረፉ፥ በድብቅ መታተሙ በዝምታ የሚታለፍ ከሆነ ያንሰራራዉን የአማርኛ ጥበበ ቃላት እጅጉን ይጐደዋል፤ ሥነፅሁፍ ግን የዉሸት ወንዝ አይንደዉም።

Published in ጥበብ

መግቢያ
ከጥቂት ጊዜያት በፊት ፌስቡክላይ በሚገኝ የአዳም ረታ አድናቂዎች ቡድን ውስጥ አንድ ሰነድ አገኘሁ፡፡ ይሄ ከሀያ ገፆች በላይ ያለው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ አዳም በተለያየ ጊዜ በአንባቢዎቹ ለተጠየቃቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጠበት መድበል ነው፡፡ ፋይሉን አንብቤ እንደጨረስኩ ይሄንን ጽሑፍ ማግኘት ላልቻሉ ሰዎች ባጋራ ማንንም እንደማይጎዳ ስላመንኩበት ነው ይሄንን ጥሑፍ ማዘጋጀቴ፡፡ ዋናው ዓላማዬ ግን ሕጽናዊነት ምንድን ነው የሚለውን ትልቅ ጥያቄ በአጭሩ ለመመለስ ያደረግሁት ደፋር ሙከራ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ የአዳምን ጽሑፍ በረጃጅሙ ወስጃለሁ፡፡ አዳም በመጻሕፍቱ ውስጥ ካስቀመጠልን ማብራሪያዎች ላይም ቀነጫጭቤያለሁ፡፡ በአጭሩ ለጋዜጣ ፅሑፍነት እንዲስማማ ማመቻቸት ስለ ነበረብኝ አንዳንድ ቦታ ላይ ብቻ ማያያዣ የሚሆኑ አረፍተ ነገሮችን፤ አንቀፆችንና ምሳሌዎችን ከማስቀመጤ በስተቀር ቀሪው የራሱ የአዳም ቃል ነው፡፡
 አዳም እና እንጀራ
እንጀራ ለአዳም የጽሑፉን ቅርፅ የሚቀዳበት ሞዴል ብቻ አይደለም፡፡ “It is more than a model. It is a metaphor” ይላል በራሱ ቃል፡፡ “ከሞዴልነት በላይ ነው፡፡ እንጀራ ተለዋጭ ዘይቤ ነው፡፡ እንጀራ ክብ ነው፡፡ ባለ ሦስት ዲሜንሽን ነው፤ ግን ደግሞ ጠፍጣፋ፡፡ ቀዳዳዎች አሉት ግን ደግሞ ልሙጥ ነው፡፡ በጠጣር እና ጠጣር ባልሆነ ቁስ መካከል የሚገኝ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የእንጀራው ቀዳዳዎች (ዐይኖቹ ማለቴ ነው) ራሳቸውን ችለው የቆሙ ይመስላሉ፤ ሆኖም ውስጥ ውስጡን ውስብስብና ረቂቅ በሆኑ ቱቦዎች የተያያዙ ናቸው፡፡ በተቃርኖዎች የተሞላ መዋቅር ኖሮትም እንኳ እነኚሁ ተቃርኖዎቹ ‘ቀጥ ብሎ እንዲቆም’ የሚያስችሉት አላባውያኑ ሆነው ይሠራሉ” (It has a contrasting structure signified by opposites and yet all contributing to its whole physical ‘survival’).
ሕይወት ራሷ ከተቃርኖዎች ውህድ የተገመደች ነች፡፡ በዚህም እንጀራ ከሕይወት/ህልውና ጋር የተቆራኘ መሆኑን ለመጠቆም አዳም የምሳሌያዊ ንግግሮቻችንን እንደ ማስረጃ ያነሳል፡፡
እንጀራውን ጋገረ፤ እንጀራ ፈላጊ፤ የእንጀራ ገመዱ ተበጠሰ፤ እንጀራ በሬው፤ እንጀራውን ያበስላል ወዘተ፡፡ ህላዌ ቅጥ አልባና የተሰደረ ሁለቱንም ነው፤ ወይም የተሰደረ ቅጥ አልባነት፡፡ (Ordered chaos እንደማለት) አንዱ ከአንዱ የተያያዘ… እንጀራ ይህንን የህላዌን ተቃርኗዊ ግንኙነቶች የሚገልፅ ምሳሌ ነው፡፡ እኔም ይሄንን ዘይቤ ወደ አጻጻፍ ስልትነት ብለጥጠው ብዙም ከዕውነታው አልራራቅም፡፡ “Existence is both chaotic and ordered; or ordered chaos. Interconnected……Injera is used as a metaphor for describing or illustrating existence. And it is not far from the truth if I stretch this metaphor into a writing technique” ይላል አዳም፡፡
እንጀራዊ/ እንጆሪያዊ ቅርፅ
ከሕጽናዊነት በፊት እንጀራዊ/እንጆሪያዊ ቅርፅ ነበር፡፡ ሆኖም የቃላት መለዋወጥ እንጂ ጠለቅ ያለ የትርጉም ልዩነት አይታይም፡፡ ምናልባት እንጀራዊ ቅርፅ የሕጽናዊነት እርሾ ወይም ሕጽናዊነት የእንጀራዊ/እንጆሪያዊ ቅርፅ እጅግ የተጠና፤ የላቀና ምልዑ በኩልዔ የሆነ ‘ቨርሽኑ’ ነው፡፡ በ”ግራጫ ቃጭሎች” መግቢያ ላይ እንጆሪያዊ ቅርፅ እንዲህ ተብራርቷል፡ “የዚህን መጽሐፍ የአጻጻፍ ቅርፁን የተዋስኩት ከእንጀራ ቅርፅ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ምዕራፎች ከእንጆሪው ጠቃጠቆ/ንዑስ ፍሬዎች ጋር ወይም ከእንጀራው ዐይኖች ጋር እንዲማሰሉ ሆኖ ነው የቀረበው (አንድ ዐይን ወይም ጠቃጠቆ አንድ ምዕራፍ) … ታዲያ በአሰያየም ውሰት ከእንጆሪ ወደ እንጀራ ከመጣን ለምን ከእንጀራ ወደ እንጆሪ አንሄድም? ከዚያ ወደዚህ የወሰደን መንገድ አይመልሰንም ማን አለ? ወደ መነሻው ሄድኩና ለዚህ ልብ ወለድ ቅርፅ እንጆሪ የተሰኘ ስያሜ ሰጠሁት ወይም መረጥኩ”፡፡
የእንጆሪ ቅርፅ ለሕጽናዊነት እንደ ጥንስስ ቢሆንም  ስሙን ይዞ መቆየት አይችልም (“የእንጀራ ቅርፅ” ካልተባለ በስተቀር)፡፡
አዳም በቅርቡ “መረቅ” የተሰኘው መጽሐፉ በሃገር ፍቅር ቴያትር ቤት ሲመረቅ፣ ከታዳሚያኑ መካከል በአንደኛው በቀረበለት አስተያየት መሠረት፤ እንጆሪ የሚለውን ቃል ምንም ዓይነት የቲዮሪ መፋለስ ስለማያስከትል ማውጣት እንደሚቻል ተናግሯል፡፡ (ይህ አስተያየት ሰጪ እንዳለው የእንጀራ ዓይኖች (ሰው ሠራሽ በመሆናቸው) አንዱ ከሌላው ያለው ርቀት ዘፈቃዳዊ ነው፤ የእንጆሪው ጠቃጠቆዎች ግን (ተፈጥሯዊ በመሆኑ) በስሌት ሊቀመጥ የሚችል ቅጥ አላቸው)፡፡
ከእንጀራ/እንጆሪያዊነት ወደ ሕጽናዊነት
አዳም ከእንጀራ/እንጆሪያዊ ቅርጽ ወደ ሕጽናዊነት ለመሸጋገር ወደ ትናንት ርቆ ይጓዛል፤ በንባቡና በማሰላሰሉ፡፡ “የድሮ ሰዎች እንደኛ ርቱእ (literal) አይደሉም፡፡ ከፊደል ገበታቸው እስከሚበሉት ነገር ብታይ የሆነ ዓይነት ለመፈታት የሚጠብቅ ሚስጥር አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ግንዛቤ ላይ ለመድረስ በሆነ ዓይነት ስነ-ውበታዊ ልምድ (aesthetic experience በሚባለው) ውስጥ አለፍኩኝ፤ ከዚያ ጊዜ በኋላ የዚያን ጠፍጣፋ ዳቦ ትርጓሜ ሳሰላስል ቆይቻለሁ”፡፡
የእንጀራን ዘፍጥረት ፀሐይ ትመለክበት ከነበረው ዘመን እንደሚነሳ ይናገራል አዳም፡፡ “እንጀራ የሚገርም ቅርፅ አለው፡፡ ዘፍጥረቱም ፀሐይ ትመለክበት ከነበረው ዘመን ይነሳል፡፡ በዚያን ዘመን ፀሐይ በክብ ምልክት ትወከል ነበር፡፡ የኛ ፊደል ፀሐዩ ‘ፀ’ የፀሐይ ወኪል ነው፡፡ ዐይኑ ‘ዐ’ም  የተባለው ፀሐይ በሰማዩ ላይ ያለች ‘ዐይን’ በመሆኗ ነበር፡፡ የእንጀራን ጉድጓዶች ‘ዐይን’ ማለታችን ገጠመኝ አይመስለኝም”፡፡
“ክብ ከጥንት ጀምሮ የሕብረት፣ የአንድነትና የዘላለማዊነት ምሳሌ ነው፡፡ መካከሉ ላይ አንድ ነጥብ ያለው ሰርከምፓንክ የሚባል ክብ ደግሞ አለ፡፡ ፀሐይን እና የፀሐይ አምላክ (ግብፅ ውስጥ “ራ” የሚባለውን) ይወክላል፡፡ (“እንጀራ” ውስጥ ያለችው “ራ” ከዚህ ጋር ግንኙነት ቢኖራትስ?) ክቡ እና ነጥቧ የወንዴና ሴቴ ኃይሎች መንፈሳዊ ውሕደት ትዕምርት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አለም አቀፋዊ ትርጓሜ ነው” (This is a universal/cosmic sensibility)፡፡   
ታዲያስ እንጀራ ስላለፈው ዘመን እንዲዘክር በዕቅድ የተወጠነ፣ የወደፊቱንስ የሚያመላክት ጽሑፍ/ሐውልት ነው ለማለት አንችልምን? (አዳም ረታ)፡፡
ስለ እንጀራ አመጣጥ ሚቶሎጂ ደግሞ እንዲህ ያትታል…
“በአንድ አምላክ መመለክ ከመጀመሩ በፊት የኖሩ ማኅበረሰቦች ለእያንዳንዱ ፍጡር እና ባሕርይ የሚያብራሩት ትረካዎች ነበሯቸው፡፡ ኃላፊነትን ሁሉ ጠቅልለው ለአንድ አምላክ ከመስጠታቸው በፊት በነበረው በዚያን ዘመን የፍጡራን እና የፍጡራኑ ግብር በጠቅላላው በሚቶችና በአፈታሪኮች የማብራራት ልማድ ነበራቸው፡፡ ከ”አዲስ ነገር” ጋዜጣ ጋር ባደረግሁት ቃለ ምልልስ የጤፍን አመጣጥ የሚያብራራ አፈታሪክ ነገር እንደማይጠፋ ተናግሬያለሁ፡፡ (ያኔ ማግኘት አልቻልኩም ነበር እንጂ)፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በለስ ቀንቶኝ ጤፍ እንዴት የኢትዮጵያዊያን ዋና ምግብ ሊሆን እንደቻለ የሚያብራራ አንድ ታሪክ አነበብኩ፡፡ አሁን የታሪኩን ዕውነተኛነት ጥያቄ ውስጥ አላስገባም፡፡ ሁሌም ቢሆን ሚቶችን ስናነብ የምናደርገው ስለ ዕውነተኛነታቸው መጨነቅ ሳይሆን ሚስጥራቸውን ፈልፍሎ ለማውጣት መጣር ነው፡፡ የተለያዩ ሕዝቦች ከላይ ሲታዩ እርባና ቢስ የሚመስሉ ጥያቄዎችን የሚመልሱባቸው ተረኮች እንዳሏቸው ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ለምንድን ነው ቀበሮ ጭራ የበዛው ጅራት ያላት? ውሻ እንዴት ለማዳ ተደረገ?  ጨረቃ ለምን በየወሩ ትመጣለች? ሰው የተፈጠረው እንዴት ነው?
የጤፉ ጉዳይ ለየት የሚያደርገው የተወሰነ አመክንዮአዊ ድባብ አለው፡፡ የሆነ ሊታመን የሚችል ነገር፡፡
እንግዲህ ይሄ ታሪክ የተከሰተው ከክርስቶስ በፊት 1500 አካባቢ ነው፡፡ ክስተቱም በእውኑ ዓለም ከነበረ ሰው ጋር ተያያዥ ነው፡፡ ይሄውም ሰው ኢስዬል፣ አጋቦስ (የንግሥና ሥም) የሚባል ኢትዮጵያዊ ንጉስ ነው፡፡ (‘አፄ’ የሚለውን የማዕረግ ሥም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመ ንጉስ)፡፡ ሌላኛው ስሙ ሰንደቅ አላማ ይባላል (ብዙ ስሞች አሉት)፡፡ ሰንደቅ አላማ ዘንዶ ንጉስ ነበር፡፡ (ይህቺ የዘንዶ አፈታሪክ ዓለም አቀፋዊ ናት)፡፡ ከሕይወት ታሪኩ እንደምንረዳው፤ ይህ ሰው ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ‘ሳይንቲስትም’ ነበር፡፡ ዘመሚትን፣ በቅሎን፣ የሜዳ አህያን የመሳሰሉ እንስሳትን ተያያዥነት ያላቸውን ዝርያዎች በማዳቀል እሱ እንደፈጠራቸው ይነገራል፡፡ ሰንደቅ አላማ በተፈጥሮ ላይ ይመሰጥ ስለነበር፣ የራሱ የሆነ የአትክልት ቦታ እና የእንስሳት ማቆያ ነበረው፡፡ ረዥም ዕድሜ ለመኖር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ለመፈልሰፍ ታድሎም ነበር፡፡ በዚህም ከ425 ዓመታት በላይ መኖር ችሏል፡፡ የሚበላውና የሚጠጣው ሁሉ ከሰው የተለየ እንደነበር ይነገራል፡፡ የሚጠጣው ውሃ ከአለቶች መካከል ከሚፈልቅ ምንጭ ይቀዳል፤ ‘የሕይወት ውሃ’ ነበር የሚባለው፡፡ እያደር ወጣት የሚያደርግ ኃይል ያለው ድንጋይ ላይም ይተኛ ነበር፡፡
ሰንደቅ ዓላማ 425 ዓመታትን ከኖረ በኋላ ግን ሕይወት ሰለቸችውና መሞት ፈለገ፡፡ አንዲት ወጣት ልዣገረድ እንድትገድለውም አደረገ፡፡ አፄውን የገደለችው ይህች ወጣት ኋላ ላይ ንግሥት ማክዳ/ሳባ ሆነች፡፡ የቀደመ ስሟ ኢተያ/እትዬ/እቴጌ ነበር… ሳባ እንግዲህ ‘እቴጌ’ ተብሎ ለመጠራት የመጀመሪያዋ ንግሥት ነች፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ አላለቀም፡፡ እሱ ከሞተ በኋላ ሳባ ንግሥት ሆነች፡፡ በዘመነ መንግሥቷም ረሃብ በመላ አገሪቷ ተስፋፋ፡፡ የተራቡ ወገኖቿን መመገብ ያቃታት ሳባ፣ የሰንደቅ ዓላማ መቃብር ዘንድ ሄዳ አነባች፤ ፀሎት አደረሰችም፡፡
በሕልሟም እግዚአብሔር ቀርቦ በንጉሱ መቃብር ላይ ከሚበቅለው ሣር በሚገኘው ፍሬ ሕዝቧን እንድትመግብ ነገራት፡፡ እንደተነገረችው አደረገች፡፡ ያ የሣር ፍሬ ጤፍ ነበር፡፡ ‘ጤፍ’ ማለት ትርጉሙ ‘ጣፋጭ’ እና ‘የተትረፈረፈ ምርት’ ማለት ነው፡፡ ጤፍ ዝናዋ ገናን የሆነ ፍሬ ነበረች፤ ስለ እሷ በመስማት ብቻ ንጉስ ዳዊት የምወድስ ግጥም ጽፏል፡፡
ሰንደቅ ዓላማ ባዮሎጂስት የነበረ መሆኑ የጤፍ ግኝት የአጋጣሚ ነገር አይመስልም… ምናልባትም ንጉሱ ራሱ ይሆን ይሆናል መጀመሪያም ጤፍን ያገኘው፤ የማክዳ ተረት ነጋሪዎች ይሆናሉ የፀሎቷን፣ ሕዝብ የመመገቧንና የእግዜርን ነገር ያከሉበት፡፡ እንደው ነገሩ እንዲህ እንኳ ባይሆን፣ ጤፍ እንዲህ ባለ ንጉስ መቃብር ላይ መብቀሏ በራሱ እየሞተ ካለ የንጉሱ ገላ ረዥም ዕድሜ የመኖር ምስጢርን እየወረሰች ይመስልባታል”፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለች የተጀመረችው ጤፍ እንግዲህ ረዥም ዕድሜ መቆየት ብቻ ሳይሆን እንጀራ  በመሆን ዘላለማዊ ሆናለች፡፡ አዳምም እንጀራ ምግብ ብቻ ሳይሆን፤ እንጀራ የአጻጻፍ ስልቴን የቀዳሁበት ሞዴል ብቻ ሳይሆን፤ እንጀራ ዘይቤ ብቻ ሳይሆን እናት ዘይቤም (root metaphor) ነው ይላል፡፡
“እናት ዘይቤ ማለት…” ይላል አዳም “እናት ዘይቤ ማለት በአንድ ቋንቋ ወይም ባሕል ውስጥ በጥልቅ በመስረጉ ዘይቤ መሆኑ ከነጭራሹ ልብ እንኳ የማይባል ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከውስጡ ሌሎች ዘይቤዎች የሚወጡበት አንድ ዘይቤ ነው ሲሉ ይተረጉሙታል”፡፡ መቸስ እንጀራ ከዕለት ዕለት ተግተን የምናላምጠው ቋሚ ምግባችን እንደመሆኑ እንደ አዳም ቀንቶን “በሆነ ዓይነት ስነ-ውበታዊ ልምድ” ውስጥ ካላለፍን በቀር አንድም ጊዜ እንኳን አይደለም ሚስጥራዊ ዘይቤነቱ አመጣጡ እንኳን አስጨንቆን አያውቅም፡፡ ለዚህም ነው እንጀራ እናት ዘይቤ (root metaphor) ነው የሚለው አዳም፡፡
አዳም ይቀጥላል… “የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ዝርዝር ጉዳዮቻችንን በዚህ የእንጀራ ዘይቤ ማብራራት እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄን የምናደርግበት አንዱ መስክ ልቦለድ በመጻፍ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እየሠራሁበት ያለውን ይሄ ዓይነቱን አጻጻፍ ደግሞ ‘ሕጽናዊነት’ እለዋለሁ”፡፡
“ሕጽናዊነት”፡ የቃሉ አፈጣጠር/አመጣጥ
ሕጽናዊነት እና ዘይቤ ምን አገናኘው ብሎ የሚጠይቅ ይኖር ይሆናል፡፡ ‘ሕጽን’ የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም በሁለት ፊደሎች መካከል ያለው ክፍተት ማለት ነው፡፡ ጽሑፍ ሊነበብ የሚችለው ይሄ ባዶ ቦታ በየፊደላቱ መካከል በመኖሩ ምክንያት ነው፡፡ በፊደል ገበታ ውስጥ ያሉት ክፍት ቦታዎች ደግሞ ማሕጸን ይሰኛሉ፡፡
ሁለቱም ቃላት የተወሰነ የትርጉም መመሳሰል አላቸው፡፡ እነኚህ ባዶ ቦታዎች ከእንጀራ ዐይን ጋር በይዘት መመሳሰል እንዳለባቸው ነው የሚገባኝ፡፡ የሕጽናዊነት ዓላማ ይሄንን ባዶ ቦታ መሙላት ነው፡፡ የሚነበበው ነገር መሙያው ነው፤ አዲሱ ጽሑፍ ማለት ነው፡፡ ከ”አዲስ ነገር” ጋዜጣ ጋር ባደረግሁት ቃለ ምልልስ ይሄንን ነገር ‘ኢንተርቴክስቹዋሊቲ’ ብዬ አስቀምጬው ነበር፡፡ ይሄን ያደረግኩት ግን በወቅቱ ሕጽናዊነትን የሚያክል ተስማሚ ቃል ባለማግኘቴ ነበር፡፡
ገሃዱን ዓለም በማንፀባረቅ ረገድ አንድ ወጥ የሆነ ትረካ ሕጽናዊ ከሆነው ይሻላል ወይስ አይሻልም የሚለው ጥያቄም ነበር፡፡ ከ”እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” [እ.ሎ.ሽ.] በፊት የጻፍኳቸውን ታሪኮች አሁን ላይ ሆኜ ሳያቸው የተሟሉ አይደሉም፡፡ ሕጽናዊነት በዚህ ረገድ የቀድሞ እኔነቴን በራሴ የለካሁበት/የሄስኩበት ስልት ነው፡፡ (“Hisinawinet” in this case becomes a critique of my earlier self)
ሕጽናዊነት የአንዱ ከሌላው መያያዝ ነው… ራሳቸውን እንደ ደሴት የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ፡፡ ከላይ ሲታይ የተለዩ ይመስሉ ይሆናል፤ በጥልቅ ላጠናቸው ግን ሰዎች እርስ በራስ የተጠላለፉ/የተቆራኙ/የተዛመዱ ናቸው… በዘር፣ በቋንቋ፣ እልፍ የባሕል እሴቶችን በመጋራትም”፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸውን መረባዊ ግንኙነት ማሳየት የሕጽናዊነት አንዱ ግብ መሆኑ በአዲሱ መጽሐፍ “መረቅ” ውስጥ እንዲህ ተቀምጧል፡ “በሕጽናዊነት አመለካከት በሰው ልጆች መሃል ያለው የግንኙነት መስመር ቀጥተኛ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው በግልጽም ይሁን በሕቡዕ መረባዊ መሆኑን ማንሳት ነው” (ገጽ 599)፡፡
አዳም ቀጥሏል… “የሕዳግ ማስታወሻ የሚያገለግለው እነኚህን መረባዊ ግንኙነቶች ጠቅልሎ በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ ለማካተት ነው፡፡ በእ.ሎ.ሽ. ከበደ ሚካኤልን ሳጣቅስ የእሳቸውን ፖለቲካዊ አቋም እደግፋለሁ ማለት አይደለም ወይም ደግሞ ባሕልን እንደሳቸው ሁሉ በወግ አጥባቂ ዐይን እቃኛለሁ ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ የእሳቸውን ያክል መልከ መልካም ነኝ ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ ሎሚ ሽታን ወይም የፍቅረስላሴን ልጅ ታደሠን ያውቁታል ማለት አይደለም ወዘተ…  የባሕል መረቡ በቀስታ ተስፋፍቶ እዚያች ደረጃ ድረስ እንዴት እንደሚደርስ ለማሳየት ብቻ ነው፡፡ (showing how cultural network can percolate and present itself to that minute depth)
ታዲያ ከሌላ ደራሲ ሥራ የተወሰደን አጭር ተረክ በአንድ ወጥ በሆነ ልቦለድ ውስጥ መጠቀም አዲሱን ታሪክ የፊተኛው ጥገኛ፤ በራሱ መቆም የማይችል፤ ክፍተት ያለበት አያደርገውም? ብሎ ለሚጠይቅ ቅን አንባቢ፣ አዳም ይሄንን ይመልሳል… “እቴሜቴ ውስጥ ያካተትኩትን ያን የከበደ ሚካኤልን ተረት [በማር ጠብታ ውስጥ ስለሰጠሙ ሕዝቦች የሚተርከውን] ቆርጬ ባወጣው እንኳ ልቦለዴ ያለምንም የይዘትም ሆነ የሴራ እንከን ፍሰቱን ይቀጥላል”፡፡
አንዳንድ የሕጽናዊነት መገለጫዎች
ከሕጽናዊነት መገለጫዎች አንዱ ኢንተርቴክስቹዋሊቲ ነው፡፡ ኢንተርቴክስቹዋሊቲ ማለት በቀላሉ በአንድ ትረካ ውስጥ ሌላ ገጠመኝ፣ ሌላ ልቦለድ፣ የታሪክ አጋጣሚ ወዘተ ሲጠቀስ ማለት ነው፡፡ የዚሁ ትርጓሜ ተመሳሳይ የሆነው ኢንትራቴክስቹዋሊቲም መነሳት ይኖርበታል፡፡ የሁለቱ ልዩነት በአጭሩ ሲቀመጥ፤ የመጀመሪያው አንድ ደራሲ  የሌላን ደራሲ/ገጣሚ ሥራ (የዕውንም ይሁን ምናባዊ)፤ ከዕውነታው ዓለም የተቀዳ ገጠመኝ፤ የጋዜጣ ጽሑፍ ወዘተ ሲጠቀም ሲሆን ሁለተኛው ድሞ አንድ ደራሲ የራሱን ቀደምት ሥራዎች ሲያጣቅስ ማለት ነው፡፡
“ብዙ የተማረ ዜጋ/ብዙ ያነበበ ዜጋ ባላቸው አገሮች ዋቤ ሳይጠቅሱ (የዕውነት ያለን) ጽሑፍ ማጣቀስ የተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱም ያ ጽሑፍ የሌላ ሰው እንደሆነ ይሄኛው ደራሲ ግን እንደ ወሽመጥ እየተጠቀመው ወይ ደሞ እየተረበው እንደሆነ አንባቢው ያውቃል፡፡
በእኛ አገር ግን አለመግባባትን ለማስወገድ በሕዳግ ማስታወሻ መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ አለመግባባቱም ሁለት ዓይነት መልክ ሊኖረው ይችላል፡
አንደኛው አንዳንድ አንባቢ (በቅን ልቦናም ይሁን በተንኮል) ያ የተወሰደው ጽሑፍ የተሰረቀ ነው ብሎ ሊያስብ ስለሚችል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንባቢው የተጣቀሰው ጽሑፍ ዓላማ ላይገባው ስለሚችል ነው፡፡ አንባቢው ይሄን መረዳት ካልቻለ ደግሞ አንዱ የኢንተርቴክስቹዋሊቲ ግብ ልቦለድን ወደ ዕውነታዊ ክዋኔ ማምጣት (bring fiction as experience) ተኮላሸ ማለት ነው”፡፡
ከላይ የተጠቀሰውን በምሳሌ እንመልከት፡፡ ደራሲው በእ.ሎ.ሽ. “በማር ጠብታ ውስጥ ስለሰጠሙ ሕዝቦች አንብቤያለሁ” ሲል በሕዳግ ማስታወሻ የከበደ ሚካኤል ታሪክ እንደሆነ ገልፆዋል፡፡ በ”መረቅ”ም “ግቡ እናንተ ተስፋ ያልቆረጣችሁ” (ገጽ 73) ሲል ከዳንቴ “ዲቫይን ኮሜዲ” እንደወሰደው ጠቅሷል፡፡ በሌላ መልኩ ማንም ያነበበው፤ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ታሪክ ነው ብሎ በማሰብ፤ ማንም “ባለ ቅን ልቦና” ወይ “ሴረኛ” የተሠረቀ (plagiarized)  ነው እንደማይለው በማመን፤ እንዲሁም ልቦለድን ወደ ዕውነታዊ ክዋኔ ለማምጣት (to bring fiction as experience) የፊታውራሪ መሸሻን፤ የሰብለን፣ የበዛብህን እንዲሁም የእንቆጳን ታሪክ (አንዳንድ ለውጦች ተደርገውባቸው) እንዲሁ በ”መረቅ” ውስጥ ተጠቅሟቸዋል፡፡
አዳም ከቲዮሪ ባሻገር በሥራዎቹ ኢንተርቴክስቹዋሊቲን ብቻ ሳይሆን ኢንትራቴክስቹዋሊቲንም ይጠቀማል፡፡ በየመጽሐፎቹ ውስጥ እዚህም እዚያም የሚገኙት የግጥምና የዘፈን ስንኞች፤ ቦታቸውን እንዳገኙ ሁሉ ስክት የሚሉት የግዕዝ ሀረጋት፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፤ ምናባዊ ማጣቀሻ መጻሕፍቱ እና የጋዜጣና የመጽሔት ቃለ ምልልሶች ወዘተ የኢንተርቴክስቹዋሊቲ አብነቶች ናቸው፡፡ በሌላ መልኩ በአዳም ልዩ ልዩ መጻሕፍት መካከል እንዲሁም በአንድ የአዳም መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ትረካዎች መካከል ያሉ እንደ ዘሀ የቀጠኑ የግንኙነት መስመሮች የኢንትራቴክስቹዋሊቲ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በ”ሕማማት እና በገና” ውስጥ ያለው ትንሽ ልጅ (የብርሃኑ ጓደኛ) “አለሙ” የተሰኘ የቤት ስም አለው፡፡ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” (ይ.መ.ያ.መ.) ላይ ያለው ዋና ገፀ ባሕሪ “አለሙ” ይሰኛል፡፡
ሁለቱም የሸማኔ ልጆች መሆናቸው የአጋጣሚ ነገር ይመስላችኋል? በ”መረቅ” ውስጥ በጨረፍታ ዳሰስ የተደረገችው ሊሊና የዚታዎ ሾፌር የሆኑት ጓደኛዋ ዘርአብሩክ በኩሳንኩስ ውስጥ አንድ የታሪክ አንጓ ተሰጥቷቸው አልተተረኩምን? የ”ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገዱ” ሸገኔ “መረቅ” ውስጥ ተጠቅሶ የለምን? እ.ሎ.ሽ. “ጉርሻ ተሻጋሪ ነው” በምትል ቀጭን መስመር ከ”መረቅ” አልተዛመደም? በይ.መ.ያ.መ. በእያንዳንዱ ትረካ ላይ ብቅ የሚለው ያ ጃን አሞራ በታሪኮቹ መካከል ትስስር አልፈጠረም? በእ.ሎ.ሽ. ውስጥ የሚገኙ ታሪኮችስ አንዳቸው ከሌላቸው በገጸ ባህርያቱ የትውውቅ  እና የዝምድና መረብ የተጠላለፉ አይደሉ? “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” ውስጥ “ለብሮት” የሚለው ታሪክ ገጸ ባሕሪ ትርንጎ፤ በ”ሕማማት እና በገና” “የሳር ልጆች” ውስጥ ተመልሳ አልመጣችም? ብዙ ብዙ፡፡ ይሄ እንግዲህ በእኔ አቅም ሊታይ የቻለ ትስስር ነው፤ ጊዜውን ሰጥቶ በጥልቀትና በጥንቃቄ ለሚያጠናው ሰው ከዚህም በላይ ግንኙነቶችን መጥቀስ እንደሚቻል እርግጠኛ ነኝ፡፡

Published in ጥበብ

    በአሜሪካ የሚኖረው ታዋቂው ትውልደ ኢትዮጵያዊ የምግብ ዝግጅት ባለሙያ ሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን ‘ማርከስ ኦፍ ዲዩቲ፣ ዘ ሬሲፔስ አይ ኩክ አት ሆም’ የተሰኘ አዲስ የምግብ ዝግጅት መጽሃፍ ሊያወጣ ነው፡፡የተለያዩ አገራት ምግቦችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ሳሙኤልሰን፤ ከዚህ በፊት ለንባብ ያበቃቸው መጽሃፍት ከፍተኛ ሽያጭ እንዳገኙለት ያስታወሰው ታዲያስ መጽሄት፣ አሁን ደግሞ በአዲስ መልኩ ያዘጋጀውን የምግብ አሰራር የያዘ መጽሃፉን ለንባብ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ዘግቧል፡፡ዋይት ሃውስን ጨምሮ በከፍተኛ ቦታዎችና በታላላቅ ስነ ስርዓቶች ላይ ምግብ በማሰናዳት  የሚታወቀው ሳሙኤልሰን፤ ‘ሬድ ሮስተር’ የተባለ ታዋቂ ሬስቶራንት ከፍቶ በአሜሪካ እየሰራ እንደሚገኝ ዘገባው ጨምሮ አስታውቋል፡፡

     በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለአድማጭ ጆሮ የደረሱት የድምፃዊ ደምስ ዴሲሳ “ከሚሴ አሪመሩ”፣ “ጅማአሻ” እና “አንሲመሌ” የተሰኙ ሶስት ነጠላ ዜማዎች ተወዳጅነትን እንዳተረፉለት ድምፃዊው ተናገረ፡፡
“ከሚሴ አሪመሩ” የተባለው በወሎ ከሚሴ ስልት የተሰራው የፍቅር ዘፈን ይበልጥ እንደተወደደለት የገለጸው ድምፃዊው፤ የነጠላ ዜማዎቹ ተቀባይነት ሙሉ አልበሙን ለመስራት እንዳበረታታው ገልጿል፡፡
ዜማና ግጥማቸው በታዋቂው የባህል ድምፃዊ ሰማኸኝ በለውና ሙሉጌታ ዜና የተሰሩት ነጠላ ዜማዎቹ በሙሉጌታ ዜና ተቀናብረው በዮናስ መሃሪ መዋሃዳቸው ታውቋል፡፡ ድምፃዊ ደምስ ዴሲሳ ከዚህ ቀደም የመጀመርያ ሙሉ አልበሙን ለአድማጭ ማድረሱ ይታወቃል፡፡

Page 4 of 15