ከከተማዋ ነዋሪ ውስጥ ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚሆነው ሜዳ ላይ ይፀዳዳል

ለ62 ዓመታት አዲስ አበባን ኖረውባታል፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የሚያውቋት ይህቺው ከተማ በዘመን ብዛት እየዘመነች፣ እያደገችና እየተሻሻለች መሆኗን ባይክዱም በንጽህናዋ ረገድ ዕለት ተዕለት ቁልቁል መሄዷ ሁሌም ያስገርማቸዋል፡፡ በተለይ በተለይ ልጅነታቸውን ያሳለፉበትንና ወጣትነታቸውን ያጣጣሙበትን የከተማዋን እምብርት ፒያሣን ፈጽመው አይዘነጉትም፡፡
በዘመናቸው አራዳ እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት እኒህ አካባቢዎች፣ እንደሣቸው ባሉ ዘመነኞች እጅግ ይዘወተሩ ነበር፡፡ አካባቢዎቹ የመጠጥ እና የጭፈራ ቤቶች የሚበዙባቸው ሥፍራዎች ቢሆኑም ሁልጊዜም ንፁህና ለአይን ማራኪ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ “አራዳው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዙሪያ የነበሩ የመናፈሻ ሥፍራዎች የስንቶቻችን መቀጣጠሪያና የእርቅ ሽምግልና መፈፀሚያ ቦታ ነበር መሰለሽ፤ ያኔ እንዲህ እንደዛሬው ቅጥ አንባሩ የጠፋበት ዘመን አልነበረም፡፡ ያኔ እንዲህ እንደአሁኑ በቤተክርስቲያን ደጃፍ እንደልብ መፀዳዳት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር፡፡ በየጥጋጥጉና በየሜዳው የሚፀዳዱ ሰዎችን ይዘው የሚያስቀጡ ደመወዝተኛ የሚባሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ግን ህብረተሰቡም እራሱ ፈሪሃ እግዚአሃብሔር ያደረበት፣ ሜዳ ላይ መፀዳዳት የሚያሳፍረውና እርስበርሱ የሚከባበር ስለነበር ከተማዋ እንዲህ እንደዛሬው የህዝብ መፀዳጃ ቤት አትመስልም፡፡ አሁን አሁንማ አፍንጫው ሥር ሲፀዳዳ እፍረት የማይሰማውን የከተማ ነዋሪ ማዘጋጃ ቤቱ የሚያበረታታውና አይዞህ የሚለው ይመስላል። ማዘጋጃ ቤቱ እንኳንስ የከተማዋን ጽዳትና ውበት ሊጠብቅና ሊቆጣጠር ቀርቶ የራሱን ደጃፍ ከህዝብ መፀዳጃ ቦታነት ሊከለክልና ሊያስጥል አልቻለም። አላሙዲን የልጆቻችን ኳስ መጫወቻ የነበረውን ሰፊ ሜዳ ወስደው ሲያጥሩ እንዴት ያለ ሆቴልና መዝናኛ ቦታ ሠርተው አካባቢውን ሊያሣምሩልን ነው፡፡ ተመስገን አይናችን ጥሩ ነገር ሊያይ ነው ብለን ተደስተን ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡ ይኸው ሃያ ዓመት ሙሉ በአጥር ተከልሎ የመፀዳጃና የመዳሪያ ቦታ ሆኗል፡፡ እኔ የሚገርመኝ ማዘጋጃ ቤቱ እዚሁ ዓይኑ ሥር ያለውን የሠገራ ክምር ማጽዳት አቅቶት፣ የከተማ ጽዳት፣ የአካባቢ ጽዳት እያለ መለፍለፉ ነው፡፡ ለነገሩ የሰው አይን ላይ ያለች ጉድፍ እንደሚታይሽ በራስሽ ፊት ላይ ያለው ትልቅ ግንድ መች ይታይሻል።”
 ገዳም ሰፈር ተወልደው ላደጉትና የከተማዋ ጽዳት በእጅጉ ለሚያሳስባቸው አቶ አሰፋ ታዬ፤ የከተማዋ አስተዳደር የከተማዋን ንጽህናና ጽዳት በመጠበቁ ረገድ ምን እየሠራ እንደሆኑ ፈጽሞ አይገባቸውም። በከተማዋ ዋና ዋና ጐዳናዎች ላይ ተከምረው ሃላፊ አግዳሚውን የሚያሰቅቁ የቆሻሻ ክምሮች ማንን እየጠበቁ እንደሆነም ግራ ይገባቸዋል። “የድሮዎቹ ደመወዝተኞች የአካባቢውን ንጽህና ለመጠበቅና ህብረተሰቡ በተገቢው ቦታ መፀዳዳት እንዳለበት በማስተማሩ ረገድ ሰፊ ሥራን ይሰሩ ነበር። የዛሬዎቹ ደንብ አስከባሪዎች ግን ከሱቅ በደረቴዎች ጋር ሌባና ፖሊስ ሲጫወቱ ነው የሚውሉት፡፡ ‘መሽናት ክልክል ነው’ ብሎ በመፃፍና በመለጠፍ ብቻ ምንም ለውጥ ማምጣት አይቻልም። የግንዛቤ ለውጥ ለማምጣት መስራት አለበት፡፡ እንደውም እኮ ሰው የሚፀዳዳው “መሽናት ክልክል ነው” የሚሉ ጽሑፎች በተለጠፋባቸው ቦታዎች ላይ ነው፡፡
እናም ባለስልጣናቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ቢያስቡበት ጥሩ ነው፡፡ ፎቅና መንገድ መሥራት ብቻ አንድን ከተማ ሊያሣድጋት አይችልም፡፡ ንጽህናዋም ወሳኝ ነው፡፡ የከተማዋ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ካልሰራ በስተቀር አሁን እንዲህ ከፍተኛ ወጪ እየወጣበት የሚሰራውና ብዙ የተባለለት አዲሱ የባቡር ሐዲድ መፀዳጃ ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለንም፡፡” የአቶ አሰፋን ትዝብትና ሥጋት የሚጋሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥር በርከት ያለ ነው፡፡ ከተማዋ ያለ ፕላን የተሰሩ መንገዶችና ቤቶች የሚበዙባት፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች በአግባቡ ያልተሰራባትና አሮጌ መንደሮች የተበራከቱባት እንደመሆኗ በቂ የመፀዳጃ ቤቶች የሏትም፡፡ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ የሚፀዳዳው በየመንገዱና በየጥጋጥጉ ላይ ነው፡፡
የህብረቱ መቀመጫ፣ የአፍሪካ መዲና፣ የታላላቅ አለምአቀፋዊ ድርጅቶችና ሆቴሎች መናኸሪያ እየተባለች የምትሞካሻው ከተማችን አዲስ አበባ፤ እጅግ ደካማ የንጽህና አጠባበቅ እንዳላትና በሚሊዮን የሚቆጠረው ነዋሪ ህዝቧ ዛሬም በሜዳ ላይ እንደሚፀዳዳ አንድ መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይፋ ያደረገው ይኸው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በከተማዋ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖር ሲሆን ከዚህ ቁጥር ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወይንም 25 ከመቶ የሚበልጠው የከተማዋ ነዋሪ የመፀዳጃ ቤት የለውም፡፡ ይኸው መፀዳጃ ቤት አልባ የከተማዋ ነዋሪ በየመንገዱ ላይ እና በየቤቶቹ ጥጋጥግ ይፀዳዳል፡፡
የመኖሪያ ቤቶች ተጠጋግተው በተሰሩባቸውና እጅግ በርካታ ህዝብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች፣ ነዋሪዎቹ በአብዛኛው የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ለማግኘት አለመቻላቸውን መረጃው አመልክቶ ሜዳ ላይ የመፀዳዳት ሂደቱም በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ጐልቶ እንደሚታይ ጠቁሟል፡፡
ይህንን ችግር ለማስወገድ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር መተባበርና በሜዳ ላይ መፀዳዳት እጅግ አሣፋሪ ተግባር እንደሆነ ተገንዝቦ፣ ከድርጊቱ መቆጠብ ይገባዋል ሲልም መረጃው አመላክቷል። ለነዋሪው ህብረተሰብ በቂ የመፀዳጃ ቤት ሊገነባ እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡
ሰሞኑን በ(Wash Ethiopia movement) አስተባባሪነት በአዳማ ከተማ ውስጥ በተከበረው አምስተኛው አገር አቀፍ የሃይጂንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ፌስቲቫልና አለም አቀፍ የመፀዳጃ ቤት ቀን በዓል ላይ እንደተገለፀው፤ በአገሪቱ ከ60-80 በመቶ የሚሆነው የጤና ችግር ተላላፊ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ደግሞ 75 በመቶ የሚሆነው በንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረትና በአካባቢ ንፅህና ጉድለት ሣቢያ የሚከሰት ነው፡፡ በአገራችን የህፃናት ገዳይ በሽታዎች ከሆኑ የጤና ችግሮች መካከል ግንባር ቀደም የሆነው የተቅማጥ በሽታም ከንፅህና ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚከሰት እንደሆነ ተጠቁሞ፤ በአፍሪካ ከንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረትና ከግልና ከአካባቢ ንፅህና ችግር ጋር በተያያዙ የጤና ችግሮች በየሰዓቱ 115 ሰዎች እንደሚሞቱ በዚሁ ፌስቲቫል ላይ ተገልጿል፡፡
የአገሪቱ ርዕሰ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ፤ በዚህ መልኩ ሜዳ ላይ የሚፀዳዳ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንዳለባት ስሰማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ የምትገኘው የዶርዜ ሃይዞና የሸበዲኖ ወረዳ ነዋሪዎች ይህንን ሲሰሙ ምን እንደሚሉ ማሰቡ አቃተኝ፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች እጅግ አሣፋሪው ተግባር ሜዳ ላይ መፀዳዳት ነው፡፡ እነዚህ ቦታዎች “ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት የነፃ” (Open deification Free) ተብለው በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ሜዳ ላይ መፀዳዳት እጅግ አሣፋሪ ተግባር መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህንን አሣፋሪ ተግባር ላለመፈፀም በእጅጉ ይጠናቀቃሉ፡፡ ይህንን እምነታቸውን ጥሶ መንገድ ላይ የሚፀዳዳ ሲያዩ በዝምታ አያልፉትም፡፡ ነዋሪዎቹ እንዲህ አይነት “አደጋ” በአካባቢያቸው ሲፈፀም የሚጠራሩበት የራሣቸው የሆነ የኮድ መጠራሪያ ድምፅ አላቸው። ይህንን ጥሪ የሰማ የአካባቢው ነዋሪ ሁሉ ጥሪው ወደተደረገበት ቦታ በፍጥነት ይሄዳል፡፡ ሰውየው (ሴትየዋ) መፀዳዳታቸውን እስኪጨርሱ ድረስ ይጠብቁና ሠገራውን በፕላስቲክ ከረጢት ውስጥ እንዲከት ያስገድዱታል፡፡ በሠገራው ላይ የሰውየው ሙሉ ስም ይፃፍበትና በዋናው መንገድ ላይ ይንጠለጠላል፡፡ “የእከሌ ሰገራ ነው” የሚለውን ፅሁፍ የሚያነበው የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ ለሰውየው የሚሰጠው ግምት እጅግ ያነሰና የወረደ ይሆናል፡፡ ይህም ድርጊቱን በፈፀመው ሰው ሞራልና ስብህዕና ላይ ከፍተኛ ውድቀትና በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድም መገለልን ያስከትልበታል፡፡ ማንም ሰው ይህ እንዳይደርስበት  ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት ይቆጠባል፡፡ አዲስ አበቤዎች ከዚህ ምን ይማሩ ይሆን?  

Published in ዋናው ጤና

“የመለስን ራዕይ እናስፈጽማለን” እያሉ ተጐልቶ መዋል ምንድነው?
ሰሞኑን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋለውን የፎርጅድ “ስፔሻሊስት” ጉድ ሰምታችሁልኛል? የመቶ ምናምን መስሪያ ቤቶችን ማህተም፣ ቲተር፣ ወዘተ… በመቅረፅ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ (ሳይማሩ ድግሪ እኮ ነው!)፣ መንጃ ፈቃድ፣ የጋብቻ ሰርተፊኬት፤ ውክልና፣ ሊብሬና ሌሎች ሰነዶችን “ሲያመርት” መክረሙን የሰማሁት ከኢቴቪ የፖሊስ ፕሮግራም ነው፡፡ (ፎርጅድ በፎርጅድ ሆነናላ!) ይሄኛውን የፎርጅድ “ስፔሻሊስት” ከቀድሞዎቹ ልዩ የሚያደርገው ምን መሰላችሁ? ያልደፈረው የመንግስት መስሪያ ቤትና የግል ተቋማት የለም፡፡ (አይዞህ ያለው ማነው?) የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ የፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የግል ክሊኒኮች፣ የመንግስትና የግል ዩኒቨርስቲዎች፣ ወዘተ (የማን ቀረ ታዲያ!) ማህተሞችን … ፎርጅድ እየሰራ የተለያዩ ማስረጃዎችን ያቀርባል ወይም ይቸበችባል፡፡ (ፎርጅድ ፈላጊው “በሽ” ነው ማለት እኮ ነው!)
የሚገርማችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማህተምና ቲተር እንኳን አልቀረም እኮ፡፡ የእነ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ቲተርና የኦነግን (አደጋ አለው!) ማህተምም ሲያዘጋጅ እንደነበር ተገልጿል - የፎርጅዱ ስፔሻሊስት፡፡ እኔ የምለው ግን … በ“ፎርጅድ” ሙያ የሚያሰለጥን “ስውር ተቋም” አለ እንዴ? (ከሽብርተኝነት አይለይም እኮ!?) እዚህ አገር ታሪካዊቷን ጦቢያ “ፎርጅድ” የማድረግ አሻጥር (Sabotage) ተጠንስሷል ማለት ነው?
የፎርጅዱ ስፔሻሊስት ሲገርመኝ ሰሞኑን ደግሞ በዚያው የፖሊስ ፕሮግራም ላይ የመኪና ስርቆት የፈፀመች የአዲስ አበባ ኮረዳ ተመለከትኩና በግርምት ተሞላሁ፡፡ እንዴ… ማንን እንመን ታዲያ? (በፎርጅድ ኮረዶችም ተከበናል ማለት እኮ ነው!)
እኔ የምላችሁ … ይሄ የሌብነት ጉዳይ “ፕሮፌሽናል ቢዝነስ” መሰለ እኮ! (የሌቦች ማሰልጠኛ ተቋም ተከፈተ እንዴ?) በዚሁ ሰሞን 20 የሚደርሱ ከተለያዩ ሙያዎች የተውጣጡ ግለሰቦች በፎርጅድ ሰነዶች እየተጠቀሙ፣ የአፍሪካን መዲና ሲያጭበረብሩ እንደከረሙ ፖሊስ ተናግሯል፡፡ ይታያችሁ … ከመኪና አከራዮች ውሃ የመሰለች መኪና ይከራዩና ፎርጅድ ውክልና አሰርተው
ጆሮዋን ይሏታል፡፡ የድግስ ወንበሮችና ድስቶች እንዲሁም የግንባታ ማሽኖች እየተከራዩም  ቸብችበዋል፡፡ (8ኛው ሺ ገባ እንዴ?) የእነዚህ “ቁጭ በሉዎች” ሰለባ የሆነች አንዲት እመቤት ለፖሊስ ስትናገር፤ ሌቦቹ “ያሪስ” መኪና ይዘው ወደ ቢሮዋ እንደመጡ ገልፃለች፡፡ (ያሪሷም እኮ ፎርጅድ ናት!)
ለነገሩ የዚህ የፎርጂድ ነገር በሌቦች ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በመንግስትም በተቃዋሚዎችም በምሁሩም በባለሙያውም … በሁሉም ዘንድ እየታየ ነው፡፡ ሰሞኑን አንዲት የስራ ባልደረባዬ መታወቂያዋን ለማሳደስ ወደ ቀበሌ ጐራ ብሎ የገጠማትን አጫወተችኝ፡፡ የቀበሌው ሠራተኞች ወደው ይሁን ተገደው (እነሱም አያውቁት!) የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ምስልና “የመለስን ራዕይ እናስፈፅማለን” የሚል መፈክር የተፃፈበት ቲ-ሸርት ለብሰው ተደርድረዋል-ቢሮአቸው ውስጥ፡፡ ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? ቲ-ሸርቱ ለስራ ሊነሽጣቸው (Inspire ሊያደርጋቸው) አልቻለም፡፡ እንደውም መልበሳቸውንም ሳይዘነጉት አልቀሩም፡፡ ለነገሩ የራሱ ራዕይ የሌለው ሰው “የታላቁን መሪ” ራዕይ ላስፈፅም ቢል እንዴት ይሆናል? (“የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር” አሉ!) እናም ባልደረባዬን በቅጡ ሊያስተናግዷት አልቻሉም፡፡ (መታወቂያ ማደስ እኮ ነው!) እሷ ተገትራ እነሱ ወሬያቸውን እያደሱ ነበር፡፡ የማታ ማታ ዱላ ቀረሽ ሙግት ገጥማ ነው መታወቂያዋን ያደሱላት፡፡ (የፎርጅዱ “ስፔሻሊስት” በቀን ስንት የቀበሌ መታወቂያ ያመርት ይሆን?)
በነገራችሁ ላይ አንድ ፖሊስ ኦሪጂናሉንና ፎርጅዱን የቀበሌ መታወቂያ አነፃፅረው ሲናገሩ “ፎርጅድ የሚመስለው የቀበሌው ነው” ብለዋል፡፡ (የፎርጅዱን ስፔሻሊስት ወደ ህጋዊ መስመር ማምጣት አይቻልም እንዴ?) በእርግጥ መጀመሪያ ቅጣቱን መቀበል አለበት፡፡ እናላችሁ … “የመለስን ራዕይ እናስፈፅማለን” የሚል ቲሸርት ለብሰው ወሬና ሃሜት ሲያነክቱ የሚውሉ የቀበሌና የወረዳ ሰራተኞች ሁሉ “ፎርጅድ ኢህአዴጐች” ናቸው፡፡ (ኢህአዴግም ፎርጂድ አለው እንዴ?)   
ይሄውላችሁ … በቲቪ መስኮት “ኪራይ ሰብሳቢ… ፀረ ሰላም ሃይላት፣ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ” እያሉ የሚያደነቁሩን ስንቶቹ ካድሬዎችና ባለስልጣናት ሙሰኞች ሆነው እንደተያዙ በዓይናችን በብሌኑ ዓይተናል፤ሰምተናልም፡፡ አሁን እነዚህ ምን ይባላሉ? “ፎርጂድ ባለሥልጣናት!”  (“made in” የት ይሆኑ?) አንዳንዴ ሳስበው የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ፎርጅድ ሰነዶች ብቻ ሳይሆን ፎርጅድ ተቃዋሚዎችን የሚሰሩም ሳይኖሩ አይቀሩም፡፡ ጊዜ ፊቱን ያዞረባቸው ቀን ግን ቅሌት ቀለባቸው ይሆናል፡፡ (“የህዝብ ነኝ” እያሉ ህዝብን ማታለል አደጋ አለው!)
በየጊዜው የአገሪቱ የትምህርት ጥራት “ወድቋል” ሲባል እንሰማለን አይደል?! አንድም ቀን ግን ተጠያቂው “እገሌ ነው” ብለን ደፍረን አናውቅም (እኛም ራሳችን ፎርጅድ ሳንሆን አንቀርም!) እርግጥ ነው ኢህአዴግ መራሹን መንግስት የሚወነጅሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይሄ ግን “ክሊሼ” ነው - የተሰለቸ፤ የታከተ ሰበብ! ነገርዬውን ጠልቃችሁ ስትመረምሩ ግን ዋንኞቹ ተጠያቂዎች “ፎርጅድ መምህራን” እንደሆኑ ትገነዘባላችሁ፡፡ እንዴ … ሴት ተማሪዎችን “እራት ልጋብዝሽና ስለ ግሬድሽ እንመካከር”፣ “250 ብር አምጣና ማርክ ልጨምርልህ” የሚሉ መምህራኖች እኮ በርክተዋል፡፡ እናም የትምህርት ጥራት እንጦሮጦስ የወረደው በእነዚህም “ፎርጅድ የቀለም ሰዎች” ምክንያት ነው፡፡ (መንግስትም ግን ከተጠያቂነት አያመልጥም-ጠያቂ ካለ!) የሰው ፈጠራ ወይም የጥበብ ሥራ አሊያም ሃሳብ፣ ወዘተ … መንትፈው የራሳቸው በማስመሰል እነሆ በረከት የሚሉን “ከያኒያን”ም እኮ “ፎርጂድ አርቲስቶች” ናቸው-የጦቢያ የጥበብ ቆሌ የተጣላቻቸው!
እንግዲህ ፎርጅድ ያልገባበት የህይወት ዘርፍ የለም፡፡ ለምሳሌ እዚህቹ መዲናችን ላይ የፍቅር ፎርጅድ የሚሰሩ እኮ በሽበሽ ናቸው - ከወንዱም ከሴቱም፡፡ መጀመርያ ላይ “እመቤቴ፣ ንግስቴ፤ ማሬ ወለላዬ …” እያለ የፍቅረኛውን እግር ለማጠብ የሚዳዳው የጦቢያ ወንድ፤ አግብቶ “ንብረቱ” ካደረጋት በኋላ ግን ውጭ ውጭውን ያያል፤ ኮረዳ ያማርጣል፡፡ ይሄንን እኔ “ፎርጅድ ባል” ብየዋለሁ፡፡ “ፎርጅድ ሚስቶችም” “በሽ” ናቸው!! (ዘመኑ እኮ ነው!)
ቁጥራቸው ባይበዛም መታወቂያቸው ወይም ፓስፖርታቸው ላይ “ፎርጅድ ኢትዮጵያዊ” በሚል መገለፅ ያለባቸው አንዳንድ በ “ሃሰት” የተሰሩ ዜጐችም አሉ - እዚህችው ጦቢያችን ምድር ላይ፡፡ ባለፈው ጊዜ የአገልግሎት ቀኑ (expiration date) ያለፈበት የታሸገ ምግብ ከውጭ አስመጥተው በሱፐርማርኬት ስለሚሸጡ ስግብግቦች አልሰማችሁም? እስቲ አስቡት … የተበላሹ የህፃናት ምግብና ወተት ለወገን እየሸጡ ትርፍ ማጋበስ … ምን ይባላል? እውነቴን ነው … እነዚህ ከሽብርተኞች በምንም አይለዩም፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ህሊናቸውን ለገንዘብ የሸጡ ግለሰቦች “ሆዳም” ወይም “ስግብግብ”፤ በሚል ለመግለፅ መሞከር ዝም ብሎ ቃላት ማባከን ነው፡፡ ትክክለኛው መጠሪያቸው “ፎርጅድ ኢትዮጵያውያን” ነው-ተመሳስለው የተሰሩ! (“ሃሰተኛ” ኢትዮጵያውያን እንደማለት!) በዜጐቻቸው ሰቆቃ የከበሩ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችም እንዲሁ ከዚህ የተሻለ ስም ሊሰጣቸው አይችልም፡፡ እነሱም “ፎርጅድ ኢትዮጵያውያን” ናቸው (እንደ ፎርጅድ ብር ቁጠሯቸው!) ጥፋት እንጂ ልማት የላቸውም፡፡  
እንዴ … ሰሞኑን በመከራና በችግር ተጠብሰው ከሳኡዲ እየተመለሱ ያሉት ዜጐች ለዚህ ጦስ የተዳረጉት እኮ በእነሱ ነው፡፡ እህቶቹን ሲኦል እየወረወረ በሚያጋብሰው ገንዘብ እንቅልፉን ለጥጦ የሚያድር ሰው ኢትዮጵያዊ ሊባል አይችልም … “ፎርጅድ ኢትዮጵያዊ” እንጂ!
ደሞ አሉላችሁ … እንደ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ያሉ “እንቁ ኢትዮጵያውያን”! የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ የስደተኛ ዜጐች እንግልት እንዴት እንዳንሰፈሰፋቸው አላያችሁም? በየመድረኩ በመቆርቆር ስሜት የሚያንፀባርቋቸው ንግግሮች በቂ ምስክሮች ናቸው፡፡ “ለካ ኢህአዴግ እንዲህም ያሉ ሰዎች አሉት!” (ደሞ እንዳይሰማኝ!) ከባለስልጣንነታቸው ይልቅ ሰዋዊነታቸው የሚልቅ፤ ከኢህአዴግነታቸው የበለጠ ኢትዮጵያዊነታቸው የሚጐላ ምርጥ የጦቢያ ልጅ! ከዚህ በላይ እንዳላደንቃቸው ግን “አደጋ አለው!” (ኢህአዴግ ፓርቲው እንጂ ግለሰቦች ሲሞሉ አይወድም!) ፓርቲው እኮ የተገነባው በግለሰቦች ስብስብ ነው፡፡ (ረስቶት ይሆናላ?!)

እንደ ኤሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2007 ተሸሽሎ የወጣው ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈውን ኤችአይቪ ቫይረስ ለመግታት የሚያስችለው መመሪያ እንደሚገልጸው ስርጭቱ በጊዜው በብሄራዊ ደረጃ 2.1% ሲሆን በከተማ 7.7% እና በገጠር ደግሞ 0.9%  ይገመታል፡፡ 977.394/ ያህል ሰዎች በኢትዮጵያ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩም የተሸሻለው መመሪያ የሚያመለክት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 41% ወንዶች 59% ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ ወደ 75.420/ ያህል እርጉዝ  ሴቶች ከቫይ ረሱ ጋር እንደሚኖሩም ይህ በ2007/ የወጣው መመሪያ ይገልጻል፡፡ ከፍተኛው ስርጭት የሚታየ ውም እድሜያቸው ከ15-24 አመት በሚገመቱት ሲሆን ከፍተኛውን ቁጥር በከተማም ሆነ በገጠር የሚይዙትም ሴቶች ናቸው፡፡
ኤችአይቪ ኤይድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ለ4/ አመት ያህል ከግል የህክምና ተቋማት ጋር በመስራት ላይ ይገኛል። ፕሮጀክቶቹም የተነደፉት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ሲሆን በዚህ እትም የምንመለከተው በኢትዮጵያ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያለውን እንቅስቃሴ ይሆናል፡፡
ዶ/ር ቴዎድሮስ ማለደ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የPMICT ኤችአይቪ ኤይድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችል ፕሮግራም ክሊኒካል ሜንተርና የቡድን መሪ በመሆን የሚሰሩ ናቸው፡፡እሳቸው እንደሚገልጹት የ PMICT ፕሮግራሙ በሰሜኑ አቅጣጫ የተዘረጋባቸው ቦታዎች በአማራ ክልል በደብረ ማርቆስ፣ ቡሬ እና ባህርዳር እንዲሁም በደብረብርሀን ደሴ የሚገኙ የግል የህክምና ተቋማት ናቸው፡፡ በማርቆስ፣ ባህርዳር አካባቢ በአጠቃላይ ስድስት የግል የህክምና ተቋማት በፕሮግራሙ የተካተቱ ሲሆን እነርሱም የማርቆስ መካከለኛ ክሊኒክ፣ በደብረማርቆስ ቡሬ ላይ የሚገኘው የቅ ዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ ሆስፒታል፣ በባህርዳር የጋምቢ ቲቺንግ ሆስፒታል፣ አፍላጋትና አብራክ ሆስፒታልና በጸጋ የሚባለው ከፍ ተኛ ክሊኒክ በድጋፍ ሰጪዎች አማንኝነት ከማህበሩ ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለህብረተሰቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ በማገዝ ረገድ ስልጠናዎችንና አንዳንድ የነክኒንል እና የአቅርቦት አገልግሎትን የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ያቀርባል ፡፡
በጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በፕሮጀክቱ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች በተወሰነ ጊዜ እየተዙዋዙዋሩ ያለውን አሰራር የሚጎበኙ ሲሆን የዚህ አምድ አዘጋጅም በጋራ በመጉዋዝ የተለያዩ የግል የህክምና ተቋማትን በመጎብኘት የሚከተለውን ለንባብ ብላለች፡፡
በቡሬ የቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ ሆስፒታል የ ሓል..ማ አገልግሎት በሚሰጥበት ክፍል አንድ ባልና ሚስት ከሕክምና ባለሙያ ጋር ተቀምጠዋል፡፡
“...እኔ  ስሜ ወ/ሮ ገነት ገላው ይባላል፡፡ እድሜዬ 25/ አመት ሲሆን የሁለት ልጆች እናት ነኝ፡፡ አሁን ሶስተኛውን ልጅ የአምስት ወር እርጉዝ ነኝ፡፡ ከዚህ ሆስፒታል የመጣሁት ምርመራ ለማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ የመጣሁት ለመጀ መሪያ ጊዜ ነው፡፡ አድራሻዬ ከገጠር ሲሆን በአቅራቢያዬ ባሉ የጤና ተቋ ማት ለመመርመር ከአንዴም ሶስት ጊዜ ሄጄ ላገኛቸው አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ አሁን ጽንሱ እየከበደኝ አስቸግሮኝ ወደዚህ መጣሁ፡፡
---------////-----------
“...እኔ ደረጀ ጥበቡ እባላለሁ፡፡ እድሜዬ 29/ አመት ሲሆን እስከ አምስተኛ ክፍል ተምሬአለሁ፡፡ የወ/ር ገነት ባለቤት ነኝ፡፡ ባለቤቴን ሂጂና ታከሚ ስላት ...አረ አላገኘሁዋቸውም ትላለች። ዛሬም ሄዳ የሉም ሆነ...ነገም ሄዳ የሉም ሲሆን ጊዜ ...አይ እንግዲህስ ወደ ከተማው ፈቅ ብለን ሌላ ሕክምና እንፈልግ ብዬ እኔ ነኝ ይዣት የመጣሁት፡፡ እኔ በብዙዎች ዘንድ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ችግር ሲፈጠር ስለማስተውል የእርሱዋን ሁኔታ በንቃት እከታተላለሁ፡፡ የምፈልገው አራት ልጅ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ልጅ ከወለድን በሁዋላ ስለዘላቂው መከላከያ እናስባለን፡፡ እስከአሁንም ጊዜያዊዎቹን እየተጠቀመች ነው፡፡
---------////-----------
ከላይ ሀሳባቸውን የገለጹት ባልና ሚስት ባሉበት ክፍል የሚደረገውን ምርመራ ማወቅ አለማ ወቃቸውንና የሚኖራቸውን ስሜት እንዲገልጹ ተጠይቀው ነበር፡፡ በመጀመሪያ አቶ ደረጀ የሚከተለውን ብለዋል፡፡
“...በእርግጥ አሁን ያለነው ኤችአይቪ ኤይድስ መኖር ያለመኖሩ ከሚረጋገጥበት ክፍል ነው፡፡ እኔ በበኩሌ...አለ ቢባልም ምንም ግድ የለኝም፡፡ ምክንያቱም ኑሮ የሚኖረው ወደፊት እንጂ ወደሁዋላ አይደለምና ነው፡፡ ባለፈ ነገር ከመብሰልሰል ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ጠንቅቆ ማስተዋል ይበጃል፡፡ ስለዚህ ኤችአይቪ በደምህ አለ ብባል...ምን ማድረግ እንደአለብኝ...እራሴን እንዴት መርዳት አለብኝ ብዬ ከሐኪም ጋር ተማክሬ የሚበጀውን አደርጋለሁ እንጂ ለሆነ ነገርማ ወደሁዋላ ተመልሼ ምንም አልጨነቅም፡፡ መጠንቀቅ አስቀድሞ ነበር እንጂ...”
--------////----------
የባልተቤትየዋ ወ/ሮ ገነት መልስ የሚከተለው ነው፡፡
“...ምን ችግር አለ? ባይሆን ጥሩ ነው፡፡ ከሆነ ደግሞ ምንም የሚያስጨንቅ ነገር የለም፡፡ በዚህ ጉዳይ አንተ ነህ አንቺ ነሽ መባባልም የለብንም፡፡ በቃ...የመጣውን ነገር ተቀብለን እንደአመጣጡ መሆን ነው፡፡ ምንም ችግር የለም፡፡ በእርግጥ እኔና እርሱ ሁልጊዜ እንነጋገራለን፡፡ ልጆቻችንን በጥንቃቄ ማሳደግ እንዳለብን... እራሳ ችንንም መጠበቅ እንደሚገባን...እንመካከራለን፡፡ እንግዲህ ከዚህ አልፎ ቫይረሱ በደማችን ከተገኘ ደግሞ ኑሮአችንን ሳንበትን አንተ ነህ...አንቺ ነሽ ሳንባባል እን ዲሁ እንደተዋደድን እንኖራለን፡፡”
-----------////---------
    ባልና ሚስቱ ለምክር አገልግሎት የቀረቡበት ከፍል ያገኘነው ባለሙያ ክሊኒካል ነርስ ነው፡፡ ስንታየሁ ይባላል፡፡ ስንታየሁ እንደሚገልጸው ለክትትል ከሚመጡት ውስጥ ብዙዎቹ የሚነገራቸውን የሚቀበሉ ምንም የማያስቸግሩ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ታካሚዎች ቫይረሱ በደማ ቸው ቢገኝም እንኩዋን ከቫይረሱ ነጻ የሆኑ ሕጻናትን መውለድ እንደሚገባቸው እና ለዚህ ደግሞ ዋነኛዎቹ ፈጻሚዎች መሆናቸውን አበክረን ስለምንነግራቸው በትክክል የመድሀነቱ ተጠቃሚ በመሆን ውጤት ላይ መድረስ የሚፈልጉ ይሆናሉ፡፡ በሆስፒታሉ ለዚህ አገልግሎት የሚቀርቡ ታካሚ ዎች በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌም በወር እስከ 44/ የሚደርሱ ታካሚዎች ተጠቃ ሚዎች ይሆናሉ፡፡  በእርግጥ አንዳንዶች የመደናገጥ ሁኔታ ቢታይባቸውም እኛም ባገኘነው ስል ጠና መሰረት በተቻለ መጠን የማረጋጋት ስራችንን ከሰራን በሁዋላ ወደትክክለኛው ሁኔታ እን መራቸዋለን። ሁኔታውን ትንሽ ቀደም ካለው ጊዜ ጋር ስናነጻጽረው እጅግ የተሻሻለ እና የሚያስ ደስት ባህርይ እና የስርጭት አድማሱም መቀነሱን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ታካሚ ዎች የምክር አገልግሎት ሲሰጣቸው የሚነገራቸውን የመስማት እና በትክክል የመተግበር እር ምጃን ስለሚያሳዩ ወደፊት ለሚኖረው ከኤችአይቪ ነጻ የሆነ ትውልድን የማፍራት እቅድ ተግባ ራዊነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ሌላው የህክምና ባለሙያ መወሻ መንገሻ ይባላል፡፡ እሱ እንደሚገልጸው “...ከአሁን ቀደም ያለውን ሁኔታ ከአሁኑ ጋር ስናነጻጸር ብዙ የተለዩ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌም...በአሁኑ ወቅት ታካሚዎች በሙሉ ፈቃደኘነት ...ምን ችግር አለ? በማለት የሚነገራቸውን ለመቀበል ዝግጁ ሲሆኑ ቀደም ሲል ግን እንኩዋንስ የሚነገራቸውን በጸጋ ሊቀበሉ ቀርቶ ወደምርመራው ክፍል እንኩዋን ለመግባት የሚያንገራግሩ ነበሩ። ቀደም ባለው ጊዜ አንዳንድ እናቶች እራሳ ቸውን ከማወቅ እና መፍትሔውን ከመሻት ይልቅ ችግሩን ደብቀው እራሳቸውንም ሳይረዱ የእርግዝና ውን ጊዜ ስለሚቀጥሉ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅ ለማፍራት ቸገር እንደነበር አይዘነ ጋም፡፡ አሁን የሚመጡ ታካሚዎች ግን ከእንደዚህ ያለው እምነት ተላቀው ለምክር አገል ግሎቱ በፈቃደኝነት ስለሚቀርቡ እና በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ምክር ስለሚ ቀበሉ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅ እያገኙ መሆኑ ትልቅ ልዩነት ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት እናቶች በኤችአይቪ ቫይረስ ምክንያት መሞታቸው ሙሉ በሙሉ ቀርቶአል ለማለት ባያስደፍርም በእጅጉ መቀነሱን ግን መናገር ይቻላል፡፡”
ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የስራውን እንቅስቃሴ ለመመልከት የወጣው ቡድን በየተቋማቱ ያሉትን የስራ ሁኔታዎች እና ያጋጠሙ ችግሮችን የሚመረምር ሲሆን ጉድለቱንም ለማሟላት የራሱን እርምጃ ይወስዳል። ዶ/ር ..ዎድሮስ ማለደ የቡድኑ መሪ እንደሚሉት .....በጋራ የምንንቀሳቀሰው በአሰራር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ነው፡፡ ማህበሩ ስራውን የሚሰራው እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በመሆን ከመንግስት እና ድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በመተባበር ስለሆነ ማነቆ የሚሆኑ ነገሮች በጊዜው መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ እንቀይሳለን፡፡ብዙ ጊዜ የሚገጥመው ችግር የኤችአይቪ መመርመሪያ ኪት እጥረት ሲሆን ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ የነበረ ችግር ነው፡፡ አሁን ግን ችግሩ ሙሉ በሙሉ የተቀረፈ ስለሆነ የነበረው የአሰራር ሁኔታም እየተቀየረ ያለበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህም ረገድ መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ ወስዶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ስጋትን ቀንሶአል፡፡.. ብለዋል።

Published in ላንተና ላንቺ

በብሩክ ገብረሚካኤል የተጻፈው “ንፋስ እና ንስር” የተሰኘ የግጥም መጽሐፍ ነገ ከምሽቱ 12 ሰዓት  በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ እንደሚመረቅ ገጣሚው ገለፀ፡፡ መጽሐፉ በ96 ገፆቹ፣ 77 ግጥሞች ይዟል፡፡ በኦላንድ ማተሚያ ቤት የታተመው መጽሐፍ በውጭ ሀገራት 20 ዶላር፣ በሀገር ውስጥ 35 ብር እንደሚሸጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

በመካከለኛው ምስራቅ በፐርሺያን ገልፍ ሰሜን ምእራብ ጫፍ የምትገኝ በረሀማ ነገርግን ስትራቴጂካዊ እና በነዳጅ ሀብት የበለፀገች አገር ናት። ለዜጎቿም ሆነ ለሌሎች አገሮች ዜጎች በነፃ ህክምና ትሰጣለች፡፡ የአገሪቱ ዜጎች ከመንግስታቸው ሌሎች የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን ያገኛሉ፡፡ የኩዌት ዲናር አቅም ካላቸው ገንዘቦች በቀዳሚነት የሚመደብ ሲሆን አንዱ ዲናር ሶስት ብር ከሀምሳ የአሜሪካን ዶላር ይመነዘራል፡፡ ኩዌት በህገመንግስታዊ የንጉስ ስርአት የምትመራ አገር ናት፡፡
ባለፈው ሳምንት ባዘጋጀችው ሶስተኛው የአፍሪካ አረብ ጉባኤ 34 የአገር መሪዎችን፤ 7 ምክትል ፕሬዚደንቶች፣ 71 አገሮች እና ድርጅቶች ተሳትፈዋል። የጉባኤው ዋና አጀንዳ በአፍሪካ እና በአረብ መካካል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማጠናከር ነበር። ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የኩዌት አሚር ሼክ ሰባህ አሀመድ አል ሰባህ የሁለቱ አካባቢ ህዝቦች ቆየት ያለ ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዳላቸው በመግለፅ በዝቅተኛ የወለድ መጠን የሚከፈል  በአፍሪካ አህጉር ለተለያዩ ኢንቨስትመንት የሚውል አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በቀጣዩ አምስት አመት እንደሚሰጥና ለተለያዩ የምርምር ስራዎች የሚውል  አንድ ሚሊዮን ዶላር ከኩዌት ለአፍሪካ እንደሚለግስ ቃል ገብተዋል፡፡ በሁለቱም አካባቢ ህዝቦች የምግብ ዋስትና  እና የፀጥታ እና የደህንነት ጉዳዮች  ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች  ሊሆነ እንደሚገባ በአፅንኦት የተናገሩት አሚሩ፣ ነገር ግን አንዱ ወገን እርዳታ እየሰጠ ሌላው ወገን ምንም አስተዋፅኦ የማያደርግበት አካሄድ መስተካከል እንዳለበት በንግግራቸው አስምረውበታል፡፡ የጉባኤው ትኩረት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ቢሆንም አሚሩ የሶሪያን ጉዳይ በተመለከተ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበው እስራኤል የምትወስዳቸው እርምጃዎች እንደሚያሳስቧቸው ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛው አፍሮ አረብ ጉባኤ በሊቢያዋ ስርት ከሶስት አመት በፊት ሲካሄድ ከ2001 እስከ 2016 ይተገበራሉ የተባሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው የነበረ ቢሆንም ቱኒዚያን፣ ሊቢያን፣ ግብፅን እና የመንን ያናወጠው ህዝባዊ አመፅ እና የመሪዎች ከስልጣን መውረድ  እንዲሁም እስከ አሁን የቀጠለው የሶሪያ ቀውስ ፕሮጀክቶቹ ብዙም እንዳይራመዱ ቀስፈው የያዙ ምክንያች ናቸው፡፡
ጉባኤውን በሊቀመንበርነት የመሩት የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ለቀመንበር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፣ የስደተሦች ጉዳይ የጉባኤው አጀንዳ መሆኑ ተገቢ እና ወቅታዊ እንደሆነ በመግለፅ ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ  መፍትሄ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው አስቀምጠዋል፡፡ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካለ ችግሩን መፍታት ይቻላል ያሉት አቶ ሀይለማርያም ጉዳዩ እንደ ከዚህ ቀደም ዝም ብሎ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡ የጉባኤውን ዋና አጀንዳ አስመልክቶም በአረብ በኩል ያለው አቅም እና በአፍሪካ በኩል ያሉ የተለያዩ  እምቅ ሀብቶች ሁለቱን አካባቢዎች እንደሚያስተሳስሯቸው ተናግረዋል። ከመሪዎቹ ስብሰባ ቀደም ብሎ በተካሄደው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የስደተኞችን በሚመለከት ይቋቋማል የተባለው የአፍሮ አረብ የተቀናጀ ኮሚቴ ጥሩ ውጤት ያመጣል በለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
ከጉባኤው ጎን ለጎንም ከሰላሳ በላይ ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ከግጭቶች እና ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ አጀንዳዎች አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ።  የኢትዮጲያ እና የግብፅ መሪዎች መሀመድ ሙርሲ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ተገናኝተው  ኢትዮጲያ  እየገነባች ስላለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ተወያይተዋል፡፡ የግድቡን ግንባታ አስመልክቶ በግብፅ በኩል የቀረበው ግንባታው ላይ የመሳተፍ ጥያቄ በኢትዮጲያ በኩል ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን ግድቡን አስመልክቶ በያዝነው ወር ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ካርቱም ላይ ተገናኝተው ውይይት ያደረጉ ሲሆን ቀጣዩ ስብሰባም  በታህሳስ ወር ካርቱም ይደረጋል፡፡
ጉባኤው ባወጣው የአቋም መግለጫ በአፍሪካ እና በአረብ አገሮች መንግስታት እና ህዝቦች መሀል የቀረበ ትስስር መፍጠር፣ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የአረ ሊግ የአፍሮ አረብ የድርጊት መርሀ ግብሮች እና ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያግዝ ግብረ ሀይል እንዲያቋቁሙ፣ የአፍሪካ እና የአረብ አገሮ የገንዘብ ተቋሞች የግሉን ዘርፍ እና  የሲቪል ማህበራትን በማጠናከር የሁለቱን አካባቢዎች የንግድ ትስስር እንዲያፋጥኑ ማስቻል፣ የአፍሪካ እና የአረብ የንግድ ምክር ቤቶች እና የኢንዱስትሪው ዘርፍ እነዲሁም ሌሎች የግል ተቋሞች ተከታታይ የሆነ የምክክር መድረኮችን በመፍጠር የሁለቱን አካባቢዎች ትስስር ለማፋጠን እገዘ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሁለቱም አካባቢዎች ያሉ መንግስታት፣ የግሉ ዘርፍ እና የሲቪል ማህበራት የግብርናውን ዘርፍ እንዲያሳድጉ ማበረታታት፣ የገጠርልማት፣ የግብርና እና የምግብ ዋስትና ላይ የሚሰሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የአረብ ሊግ ይህ የአቋም መግለጫውም ሆነ የአፍሮ አረብ የአጋርነት ስትራቴጂ ተግባራዊ እንዲሆኑ በገንዘብም ሆነ በቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል። ፍልሰትን በተመለከተም የተቋቋመው የአፍሮ አረብ የቴክኒክ እና የቅንጅት ኮሚቴንም ሆነ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ስትራቴጂዎች ሁለቱ አካባቢዎች በቅንጅት እንዲሰሩ፣ ለፈለሱ ሰዎች የደህንነትና ማህበራዊ ጥበቃ ማድረግ፣ ስደተኞችን፣ ተፈናቃዮቸችን  እንዲሁም የፈለሱ ሰዎችን ለሚቀበሉ አገሮች በተለይም ለቡርኪናፋሶ እና የመን እገዛ ማድረግ እንደሚገባና ህገወጥ ፈላሾችን ለመለየት የአፍሮ አረብ የመረጃ ልውውጥ ማእከል እንዲቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን መግለጫው ያሳያል፡፡
የባህር ላይ ውንብድና እና የካሳ ጥያቄ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የአደንዛዝ እፅ ዝውውር  እና የህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር ላይ በጋራ ለመሥራትም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
አንድ የኩዌት ከፍተኛ ባለስልጣን የፍልሰት ጉዳይ አሳሳቢ ችግር ነው ያሉ ሲሆን በጉባኤው ላይ ያነጋገርኳቸው ተንታኝም፣ የፍልሰት ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ካልተሰራበት እና መፍትሄ ካልተሰጠው የአፍሪካን እና የአረቡን አለም ግንኙነት እስከማቋረጥ ሊደርስ እንደሚችል አስቀምጠዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት ከአምስትመቶ ሺህ በላይ አፍሪካውያን ወደ አረብ አገሮች ፈልሰዋል።
ሁለቱ አካባቢዎች በፀጥታ እና አሸባሪነትን በጋራ ለመከላከል ለዚህመም መረጃ ለመለዋወጥ  የተስማሙ ሲሆን በሁለቱ አካባቢዎች ለሚገኙ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ለዜጎች አመቺ ሁኔታን በሚፈጥሩና ለደህንነታቸው ትኩረት በሰጠ መልኩ እልባት እንዲያገኝ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡  
የኩዌቱ አሚር ሼክ ሰባህ በጉባኤው መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ከፊታችን ረጅም እና አስቸጋሪ መንገድ ይጠብቀናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በሁለቱም አካባቢዎች ያለው ያለመረጋጋት ነው። ስለዚህ ያቀድናቸውን ለማሳካት ብዙ ጥረት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ርካሽ የሰው ጉልበት፣ ለእርሻ የሚውል ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ አፋጣኝ የመሰረተ ልማት ፍላጎት  ይገኛል፡፡ ይህን እድል ሁለቱም አካባቢዎች ሚዛኑን በጠበቀ የዜጎቻቸውን ፍላጎት በተከተለ መንገድ እንዴት ሊወጡት ይችላሉ የሚለው ጥያቄ ምላሽ ለግንኙነቱ ምላሽ ይሰጣል ያሉት የጉባኤው ተሳታፊ፣ በተለይ በአፍሪካ በኩል ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ግድ ይላል ይላሉ፡፡
ቀጣዩ የአፍሮ አረብ ጉባኤ በአፍሪካ እንዲዘጋጅ የተወሰነ ሲሆን ሰባተኛውን የአፍሮ አረብ ንግድ ትርኢትም  ሞሮኮ በቀጣዩ አመት እንድታስተናግድ ተወስኗል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

   ህዋዌ እና ዜድቲኢ ከተሰኙት የቻይና ኩባንያዎች፣ ለሁለት አመታት ድርድር የተካሄደበትን የ30 ቢሊዮን ብር ማስፋፊያ ፕሮጀክት እኩል ተካፍለው ሰሞኑን ሥራ እንደተጀመሩ የገለፀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በሁዋዌ የሚከናወነው የአዲስ አበባ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በስምንት ወራት እንደሚጠናቀቅ አስታወቀ፡፡
ኦፊሰሩ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በኢትዮ ቴሌኮም ዋና መስሪያ ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት አጠቃላይ የማስፋፊያ ስራው በሚሰራበት ወቅት የኔት ወርክ መቆራረጥ ሊያጋጥም እንደሚችልና ህዝቡ ይህን ሊያውቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
1.6 ቢሊዮን ዶላር (30 ቢሊዮን ብር ገደማ የተመደበበት) የማስፋፊያ ስራ 50 በመቶው በህዋዌ ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ በዜድቲኢ እንደሚሰራ የገለፁት ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ፣ ሁለቱም ኩባንያዎች እያንዳንዳቸው 18 ሚሊዮን የሞባይል መስመሮችን የሚያስተናግድ የማስፋፊያ ስራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡ የማስፋፊያው ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ፣ ኢትዮ ቴሌኮም 59 ሚሊዮን የሞባይል መስመሮችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ብለዋል -አቶ አብዱራሂም ድርድሩ ሁለት አመት የፈጀበትን ምክንያት የተጠየቁት አቶ አብዱራሂም፣ ፕሮጀክቱ እጅግ ትልቅ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
የኔትወርክ መቆራረጥ መባባሱን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ በአገሪቱ ያሉ አራት ሺህ ገደማ አንቴናዎች በመብራት እንደሚሰሩና መብራት ሲጠፋ የኔትወርክ መቆራረጥ እንደሚያጋጥም ተናግረዋል - አቶ አብዱራሂም፡፡
የኦፕቲክ ፋይበር መስመር ላይ የተበራከተው የመቆረጥ አደጋም ትልቅ እክል ሆኗል ያሉት አቶ አብዱራሂም፣ የመቆረጥ አደጋ ይደርሳል” ብለዋል፡፡ ከማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በተያያዘም፣ ስራው እስኪጠናቀቅ ድረስ የኔትዎርክ መቆራረጥ እንደሚያጋጥም አቶ አብዱራሂም ተናግረዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Saturday, 30 November 2013 11:22

የሐሜት ዙር

ድርጊቱን  ያየሁት ከ15 ቀን በፊት ነው፤ ቦታው ሻላ አዳራሽ። በቦታው የመገኘታችን ምክንያት ደግሞ የአንድ ጐረቤታችን

ልጅ ሰርግ ነበር፡፡
ከሰርጉ ቦታ የደረስነው ትንሽ ዘግይተን ስለነበር፣ አብዛኛው ቦታ እንደ እኛ በተጋበዙ እንግዶች ተሞልቷል፡፡ ለትንሽ ጊዜ

ያልተያዙ ወንበሮችን ስናፈላልግ ቆየንና፣ በመካከለኛ እድሜ ላይ የሚገኙ ሁለት ሰዎች ብቻ ያሉበት ቦታ አግኝተን

ተቀላቀልናቸው፡፡ የአጋጣሚ ነገር እኛም ሁለት ነን።
የተቀላቀልናቸው ሰዎች (ከወሬያቸው እንደሰማነው) አንዱ “ከድር” የሚባል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “ሥዩም” እንደሚባል

ተረድተናል። ከድር ሲናገር ረጋ ብሎ ነው፤ በተቃራኒው ሥዩም ግን ክልፍልፍ ቢጤ፣ መናገሩን እንጂ መደመጡን ልብ

ማለት የማያሻ፡፡ ግን ደግሞ ሁለቱንም አንድ የሚያረጋቸው ባህርይ እንደ አላቸው ተገንዝቤያለሁ፤ ሰውን መቦጨቅ፡፡
በአጋጣሚ የተቀመጥነው ለሁለት በተከፈለው የወንበር ሥርዓት በአንደኛው ዳር ነበርና አላፊ አግዳሚውን ቁልጭ

አድርጐ ያሳያል፡፡ አላፊ አግዳሚው ሁሉ ታዲያ በከድርና በሥዩም የተለያየ ታርጋ ይለጠፍበትና (ባይሰማም) መዘባበቻ

ይሆናል፡፡
ከሰርጉ ቦታ የደረስነው ከሙሽሮች ቀድመን ነበርና የእነ ከድር ጨዋታ ቀልባችንን እንደ ጥሩ ልብወለድ ሰቅዞ በመያዝ

በንቃት እናዳምጣቸው ጀመር፡፡ ለነገሩ የሚስቁበትን ምክንያት ባንረዳውም ገና ወደ እነሱ ስናመራ ከልባቸው እየሳቁ

ነበር፡፡
“መጣችልህ ደሞ…” አለ ሥዩም፤ አጭር ቀሚስ ለብሳ ተረከዙ ረጅም የሆነ ጫማ የተጫማች ቀጭን ረጅም ሴት አይቶ፡፡
“በለው” ከድር አደነቀለት፤ ግን ምኗ እንዳስደነቃቸው አልገባንም፡፡
“እስኪ ተመልከታት፤ እግር አለኝ መስሏት ነው በእግዚአብሔር… እንዲህ ሰጐን መስላ የመጣችው” ሥዩም ተናግሮ

ሳይጨርስ ከድር በሳቅ አጀበው፡፡
የከድርና የሥዩም አባባል እየገረመን ወደሚጠቋቆሙባት ሴት ዘወር ስንል እውነትም ቀጭን፣ ረጅም፣ ከመሆኗም በላይ

አፍንጫዋና ከንፈርዋ ወደፊት ሾለው ሲታዩ ጀማሪ ሰዓሊ የተጫወተባት ልዩ ፍጡር መስላ ታየችን፡፡
“እያማረ መጣልህ! ተመልከት ከእሷ ኋላ ያለችውን የማር አቁማዳ” ከድር ሲናገር ሁላችንም በሳቅ አጀብነው፡፡ ከጭኗ

እና ረጅሟ ሴት ኋላ የገባችው ደሞ በተቃራኒው አጭር ከመሆኗም ሌላ በጣም ወፍራም ስለሆነች፣ በተራመደች ቁጥር

ከሆዷ ላይ የተንጠለጠለው ስጋ ለብቻው ይንቀጠቀጣል፡፡
“አሁን እነዚህን አቅፈሃቸው ተኛ ብትባል ምን ትሆናለህ?” ሥዩም ጠየቀ፡፡
“ማ? እኔ ከድር?”
“አዎ አንተን!” ሥዩም መለሰለት፡፡
“ኧረ በአላህ ይዠሃለሁ፤ ከሁለቱ ቀርቶ ከአንዷ ጋር እንኳ ተኛ ከምባል ለአንድ ወር ያህል ወንዝ ወርደህ ውሃ እየቀዳህ

ማህበረሰቡን አገልግል ብባል ይሻለኛል”
“ለምን?”
“ያችኛዋ…” ወደ ረጅሟ እየተመለከተ “እስዋን ከማቅፍ አጋም እሾህ ላይ ተኛ ብባል ይሻለኛል። ባዶ አጥንት እኮ ናት!

ምኗን ታቅፈዋለህ? በሌላ በኩል ይች ዝተቷ በአንድ በኩል ስታቅፋት ሌላው ይዘረገፍብሃል፡፡ ወይ ደሞ መጀመሪያ

ቦርጯን ሰብስበህ በገመድ ጥፍር አርገህ ታስርና ትንሽ አካል የሚመስል ነገር ካገኘህ መሞከር ነው፤ ኧረ ሁሉም

ይቅሩብኝ” ከድር የተወሰነበት ያህል እያንገሸገሸው ሲመልስ ሁላችንንም አሳቀን፡፡
“ይልቅስ ተመልከት” ከድር ሥዩምን ወደ ሌላ ሴት ጠቆመው፡፡
የተጠቆመችው ሴት አጠር ያለ የባህል ቀሚስ ለብሳ፣ በአገር ባህል መዋቢያዎች የደመቀች ናት፤ አምባሯ፣ አልቦዋ፣ ጨረቃ

ጣልሰሟና ጉትቻዋ ሁሉ ባህላዊ ናቸው፡፡
“ምንም አትል፤ ግን ህዳሴ ቂጥ ናት” እንደታዘዝን ሁሉ ሁላችንም አንዴ በሳቅ አወካን፡፡
“ህዳሴ ቂጥ ማለት ምን ማለት ነው?” የሁለቱን ጨዋታ በአርምሞ ሲከታተል የቆየው ጓደኛዬ ጠየቀ።
“ህዳሴማ የተዝረከረከ ማለት ነው፤ ቅርጽ የሌለው” ሥዩም በልበ ሙሉነት መለሰ፡፡ “እውነቴንኮ ነው ሞፈር ታውቃለህ?

የኔ ወንድም!”
ጓደኛዬ በአንገቱ ንቅናቄ ብቻ ስለ ሞፈር እንደሚያውቅ ለሥዩም መለሰለት፡፡
“እንደዚያ ማለት ናት፤ እግዜር ሲሰራት ሞፈር ሊያረጋት አስቦ ነበር ማለት ነው፤ ሙልጭ አርጐ የጠረባት”
“ቢሆንም ከቅድሟ ድሪቶ እሷ ትሻላለች” ከድር የሥዩምን ሃሳብ የሚቃወም መልስ ሰጠ፡፡ በመሃል ከሙዚቃ ተጫዋቾች

አንዱ ወደ መድረክ ወጣና “ወለቤ፣ ወለቤ፣ የዓባይ ዳር ጉማሬ፣ ወጥቶ አደረ ዛሬ” የሚለውን የአበበ ተሰማ ዘፈን

ይዘፍን ጀመር፡፡ የሁላችንም ሃሳብ ወደ ዘፋኙ እንደ ዞረ:-
“የአባይ ዳር ጉማሬ? የምን የዓባይ ዳር ነው? የሻላ ጉማሬ አይልም? ለራሱ ነው የሚዘፍነው፤ አፉ፣ አፍንጫው፣

ውፍረቱ፣ ቀለሙ በአጠቃላይ የዓባይም ሆነ የጫሞና የሻላ ሃይቆች ጉማሬ ማለት ራሱ ነው” ሥዩም ሲናገር ከድር

አጨበጨበለት፡፡
ወዲያው አንዲት የፈረደባት አጭርና ቀጭን ሴት ወንበር ፍለጋ በአጠገባችን አለፈች፡፡ እሷም ከእነ ከድር ሽሙጥ

አላመለጠችም “ይች አሁን ሰው ናት ወይስ ከአፍ የወደቀች ጥሬ?” ሥዩም ከድርን ጠየቀው፡፡
“ሰው ተሳስቶ ሳያላምጥ የዋጣት ሽንብራ ከዘጠኝ ወር በኋላ ሰው ሆና ወጣች” ከድር የሥዩምን ሃሳብ አዳበረለት፡፡
“ይችንም ሴት ብሎ እንደኔ ያለው አንዱ መከረኛ ያገባት ይሆናል”
“እሱማ ምን ችግር አለው?” ሥዩም ጠየቀው፡፡
“እንደ ቻሌንጀር እጭኑ ላይ ፈንድታ እዳ ውስጥ ታስገባዋለቻ! ምን ነካህ ሥዩሜ! ከዚች የሚወለደውን ልጅም አስበው፤

ሰው ነው ወይስ የሳሎን ውሻ ከዚች ሊወለድ የሚችለው?” ሁለቱ ሲሳሳቁ እኛ ግን ከልብ ደነገጥን፡፡
“ይህንን ሁሉ ጉድ ብትሰማ ምን ይሰማት ይሆን?” ለመጀመሪያ ጊዜ ጠየቅሁአቸው፡፡
“ምን ይሰማታል? ከእኛ በላይ ታውቀዋለች፤ ምን ጣጣ አለው?” ሥዩም ፈጠን ብሎ መለሰልኝ፡፡
“አ…ይ የመብት፣ የሰብአዊነት ጉዳይ…” ሥዩም አላስጨረሰኝም “ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነው የመጣኸው ወንድም!

ለነገሩ እንኳንም ከሂውማን ራይትስዎች አልሆንህ እንጂ ችግር የለውም፡፡ እሱም ቢሆን ኢትዮጵያን የሚመለከታት

በአንተ ዓይን ነው”
“ማለት?” ሃሳቡ ስላልገባኝና የጨዋታውን ርዕስም ያስቀየርሁት ስለመሰለኝ ጥያቄውን አራዘምሁለት፡፡
“ሲጀመር ድሃ አገር ውስጥ እየኖርህ ስለሰብአዊ መብት ልታወራ አትችልም፤ ቅድሚያ ሆድህን ሞልተህ ማደር አለብህ፡፡

የውይይታችን መነሻ የሆነችው ሴትም የድህነት ውጤት ናት”
“የድህነት ውጤት ናት ስትል?”
“የድሃ ልጅ ስለሆነች ነዋ እንዲህ የሽንብራ እሸት አክላ የቀረችው፤ የሃብታም ልጅ ብትሆን ኖሮ ምን አይነት መለሎ

ትሆን ነበር መሰለህ” ሥዩም ሲናገር በሰው ዘር ጥናት የተረቀቀ እውቀት ያለው መስሎ ነው፡፡
“የሩቅ ምስራቅ አገር ሰዎች፤ ለምሳሌ ቻይናውያን፣ ጃፓኖች፣ ኮርያዎች…በጣም አጭሮች ናቸው፤ ድሃዎች ናቸው ማለት

ነው?”
“እኔ የማወራህ ስለ አፍሪካ ድሃዎች ነው፤ አንተ የጠቀስሃቸው ሰዎችም ቢሆኑ ችጋራሞች ነበሩ፤ ከቁመታቸው በፊት

ኢኮኖሚያቸውን ስላሳደጉ ነው፡፡ ምን አለ በለኝ ቁመታቸው ከዚህ በኋላ ያድጋል” ሁላችንም ሳቅንበት፤ ወዲያው ከድር

አቋረጠን፡፡
“ተመልከት ሥዩሜ! ኩንታል ሙሉ የበቆሎ ዱቄት በአካሏ ላይ ገልብጣ መጣችልህ” አለ ከአንድ ጐልማሳ ጋር ወደ

አዳራሹ በመግባት ላይ ወደነበረች ሴት በአገጩ እያመለከተ፡፡
“አብሯት ያለው ሰውየስ የወፍጮ ቤት ሰራተኛ መሆኑ ነው” ሥዩም እየሳቀ ጠየቀው፡፡
“ወይም በአንዱ ጐረምሳ እያስቀናችው ጆንያ አንስቶ ገልብጦባት ይሆናል፤ መቼም ሰው በጤናው አጌጣለሁ ብሎ እንዲህ

ያልተጠረገ ቋት መስሎ ሰርግ ቤት አይሄድም” ከድር ሃሳቡን አገዘፈለት፡፡
ከመሃል “ሙሽሮች እየደረሱ ስለሆነ ሁላችንም ብድግ ብለን በእልልታና በጭብጨባ እንቀበላቸው” የሚል ድምጽ

ከመድረክ አስተጋባ።
“እናጨበጭባለን እንጂ! ሥራችን ማጨብጨብ አይደል፤ ቀበሌ ጭብጨባ፣ ለስብሰባ በተጠራንበት ቦታ ሁሉ ጭብጨባ፣

ወያላ ሲሰድበን ጭብጨባ፣ ፖሊስ ሲደበድበን ጭብጨባ፣ ቺኮቻችን ሲያዋርዱን ጭብጨባ፣ በቃ ለጭብጨባ የተፈጠርን

አጨብጫቢዎች” ሥዩም በራሱ ንግግር ተበሳጨ፡፡
በጭብጨባና በእልልታ ታጅበው ሙሽሮቹ ቦታቸውን ያዙ፤
“ይች ናት እንዴ ሙሽራዋ” ከድር ሳቅ እያፈነው ጠየቀ፡፡
“የለም ተመሳሳይዋ ናት” ሥዩምም ሳቀ፡፡
“እየቀለድሁ አይደለም ሥዩሜ… እስኪ ተመልከታት፤ የራበው አዞኮ ነው የምትመስል”
“ጨዋታችሁን ሳዳምጥ ሴቶቹን ብቻ ነው የምትተቹ፤ ወንዶች ምንም ችግር የለባቸውም ማለት ነው?” ጓደኛዬ ለሁለተኛ

ጊዜ ጠየቀ፡፡
“እንደ ሴቱ አይሆኑም እንጂ ግራ የገባቸው ወንዶች ሞልተዋል፤ ግን የእኔ ወንድም በሰርግ ቀን ሴቶችን ልብ ብለህ

አስተውለሃል? ፊተ ሾጣጣ፣ ጥርሰ ገጣጣ፣ ቂጠ ሞጥሟጣ፣ ዓይነበልጣጣ ሆዷ የተዘረገፈ፣ ለምቦጯ እንደ እበት

የተጠፈጠፈ፣ ኧረ ስንቱን ቆጥሬ እገፋዋለሁ? ልብሳቸው፣ መዋቢያቸው፣ ጠቅላላ ሁኔታቸው ሁሉ ጅራቷን የተቆረጠች

እንሽላሊት ነው የሚመስሉት፤ መልሰው ሰው ሲሆኑ ይገርመኛል…” ከድር መለሰለት፡፡
የሥዩምንና የከድርን ሃሜታዊ ወግ እያዳመጥን አልፎ አልፎም እየጠየቅን ቆይተን ምሳ ለማምጣት ወደ ብፌው ቦታ

አመራን፤ ቀልባችን የወደደውን መራርጠን ከተመለስን በኋላ ምግቡም ሃሜቱም ቀጠለ፡፡
“ለዚህ ነው እንዴ ደጅ ስንጠና የዋልነው?” ሥዩም እየተመገበ፤ ግን ደግሞ የሚመገበውን ቁርጥ ያናንቅ ጀመር፡፡
“ይኸ ለውሻ አይሰጥም እንኳን በክብር ለተጠራ እንግዳ፤ እውነቴን ነው፡፡ የእነ ጐሹ ሰርግ እለት የቀረበውን ጮማ አየህ

አይደል ከድሬ!” ሥዩም ምግቡንም ከሃሜቱ ጋር እየቀላቀለ ያቀላጥፈዋል፡፡
“ካልወደድኸው መጀመሪያ ለምን ተሸከምህ? አሁንስ ማን አስገድዶህ ትበላለህ?”ልለው አማረኝና “ከነገረኛ ሰው ስንቅ

አይደባልቁም” የሚለው ብሂል ትዝ ስላለኝ ተውሁት፡፡
ከድር ስለምግቡ ምንም አስተያየት ሳይሰጥ ተመገበና እጁን በለስላሳ ወረቀት ጠራርጐ ወደ መታጠቢያ ቤት አመራ፡፡
“የዚህ ሰውዬ ነገር በጣም ይገርመኛል፤ አሁን ይኸ እስላም ነው ክርስቲያን? ብቻ ሆዱ ይሙላ እንጂ ያገኘውን ሁሉ

ጥር… ግ ነው” ሥዩም ጓደኛውን እንኳ የማይምር መሆኑን ሳውቅ ተፈጥሮው አስገረመኝ፡፡
የሐሜቱ ድር ዞሮ ዞሮ ከሃሜተኞች ጋ መድረሱም በእጅጉ አስደነቀኝ፡፡
“የእኔ ወንድም የሌለ ድንበር እናበጃለን እንጂ ሙስሊም ወይም ክርስቲያን በሬ በዓለማችን የለም” ብየው ጓደኛዬን

አስነሳሁና ወደ ሰፈራችን ተጓዝን፤ ዘወር ስንልለት ጥሬ ስጋችንን እንደሚበላው ግን እርግጠኞች ነበርን፡፡ 

Published in ህብረተሰብ

አንድም የአገር ውስጥ ባንክ እርሻችንን አልጐበኘም
ከፒቲኤ ባንክ 3 ሚ.ዶላር ተበድረን ሰርተን ከፍለናል
በቀጣዩ ዓመት የተቆላ ቡናና የማር ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንከፍታለን

ቤተሰባቸው ገበሬና ነጋዴ ነበሩ፡፡ አባታቸው የግብርና ውጤቶችን ወደ አዲስ አበባ እያመጡ፣ ከዚህ ደግሞ ሸቀጣ-ሸቀጥ

ወደ መቀሌ እየወሰዱ ይነግዱ ነበር፡፡ ቤተሰባቸውን እየረዱ ስላደጉ፣ እንደአባታቸው የመሆን ፍላጐት አደረባቸው፡፡

ስለዚህ ከጀርመን፣ ከዱባይ …፣ የተለያዩ መሳሪያዎች እያመጡ ይሸጡ ነበር፡፡ በዚህ ብቻ መወሰን አልፈለጉም፡፡
ከውጭ ዕቃዎችን ሲያስገቡ በተጓዳኝ ወደ ውጪም (ኤክስፖርት) የሚደረግ የአገር ውስጥ ምርት መኖር አለበት በማለት

አሰቡ፡፡ ለዚህ እንደ አማራጭ የወሰዱት ቡናን ነው፡፡ ስለዚህ፣ በ1988 ዓ.ም ግሪን ኮፊ የተባለ ድርጅት አቋቁመው ወደ

እርሻ እንደገቡ ይናገራሉ-የዛሬው ግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብረሃ፡፡
አቶ ታደለ ተወልደው ያደጉት መቀሌ ከተማ ነው። በትምህርት በንግድ ዲፕሎማ ሲኖራቸው፣ በዚሁ ዘርፍ የተለያዩ

ኮርሶች መውሰዳቸውን ይናገራሉ፡፡ ከ18 ዓመት በፊት ብዙ ሰው ደፍሮ ወደማይሞክረው የእርሻ ዘርፍ ገብተው ዛሬ አንቱ

የተባሉ ዘመናዊ ገበሬ ሆነዋል፡፡ ስኬትና አርአያነታቸው ለሎችም ትምህርት ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ፣ ከአቶ ታደለ ጋር

ያደረግነውን ውይይት ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡
በ1988 ዓ.ም በደቡብ ክልል በከፋ ዞን ጨና ወረዳ 1000 ሄክታር መሬት ወስደን ቡና መትከል የጀመርን የመጀመሪያው

የግል ድርጅት እኛ ነን። ከዚያ አንድ ዓመት በፊት በደቡብ ክልል ጌጄኦ ዞን በዲላ ከተማ አንድ ሄክታር መሬት ገዝተን፣

ቡና መፈልፈያ ወፍጮ አቋቁመን ነበር፡፡ ነገር ግን በአካባቢያችን የራሳችን የቡና መሬት መኖር አለበት ብለን ስላሰብን፤

ያንን የቡና መፈልፈያ፣ ለሸሪካችን በመተው ወደ ከፋ ዞረን ቡና መትከል ጀመርን፡፡
በየዓመቱ አንድ ሁለት ሄክታር መሬት እየተከልን፣ አንድ ሺውን ሄክታር በ1993 አካባቢ ጨረስነው፡፡ በወቅቱ፣ ትልቁ

የቡና እርሻ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ያሉት የግል እርሻዎች የእኛና የሚድሮክ ሲሆኑ፣ ትልቁ የእኛ ነው፡፡ የመጀመሪያውን

መሬት ቡና ተክለንበት እንደጨረስን መሬት ጠይቀን በከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ አንድ ሺህ ሄክታር ተሰጠን፡፡
ሁለት ሺውን ሄክታር መሬት አልምተን እንደጨረስን፣ በ1998 ዓ.ም፣ የደቡብ ክልል፣ ብዙ ሠራተኛ ያላቸው፤

ለኤክስፖርት አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ያደረጉ፣ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸውና

የተለያየ ድጋፍ ያደረጉ፣ በእርሻና በኢንዱስትሪ የተሳተፉ፣ … በሚል ውድድር አካሂዶ ነበር፡፡ በዚያ ውድድር እኛ በእርሻና

በአግሮ ኢንዱስትሪ አንደኛ ስለወጣን የእውቅና ሰርቲፊኬት ተሸለምን፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ደሞዝ እንከፍላለን። ለአካባቢው ኅብረተሰብ የውሃ፣ የጤናና የትምህርት፣ … አገልግሎት ድጋፍ

እናደርጋለን፡፡ ገበሬው እኛ ጋ ያየውን የቡና አተካከል፣ እቤቱ ሲመለስ ተግባራዊ ያደርጋል፣ … ምን ልበልህ ምንም

ያልነበረበት አካባቢ ከፍተኛ ለውጥ አመጣ፡፡ ዞኑም ባገኘነውና በአካባቢው በተፈጠረው ለውጥ በመደሰት ተጨማሪ 500

ሄክታር መሬት እንድናለማ ሰጠን፡፡ የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚነትና ለውጥ እየጨመረ ሄደ፡፡
እንደዚህ እያልን ከቆየ በኋላ ከሦስት ዓመት በፊት፣  የመንግሥት የቡና ተክል የነበረው የቴፒ ቡና ተክል ሊሸጥ ጨረታ

ወጣ፡፡ እኛም በጨረታው ተሳትፈን፣ ቴፒ የእርሻ ልማትን ከመንግሥት ጋር በጆይንት ቬንቸር ገዛነው፡፡ በበቃን ሚድሮክ

ወሰደው፡፡ ቴፒ ሰፊ ሲሆን ከ10ሺህ በላይ ሠራተኛ አለው፡፡ እርሻው ውስጥ ሁለት 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ስድስት አንደኛ

ደረጃ ት/ቤት፣ 10 ያህል መዋለ ሕፃናት፣ ስድስት ሳይት፣ ጤና ጣቢያ፣ ክሊኒክ፣ ፋርማሲ፣ ሆስፒታል ሁሉም ነገር

ስላለው ትልቅ ከተማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በቴፒ ከተማ እንደ ቢሮና እንደ መዝናኛ ክበብ የሚያገለግለው ትልቁ

እንግዳ ማረፊያ የእኛ ነው፡፡
እስከዚያ ድረስ ምንም ችግር አልገጠማችሁም?    
ኦ! በዘዴና ብርታት አለፍነው እንጂ በተለይ በ1993/94 ዓ.ም ከፍተኛ የገንዘብ ጥረት አጋጥሞን ነበር፡፡ በዚያን ዘመን

ከባንክ ብድር ጠይቀን ነበር። ባንክ ለእርሻ ብድር ስለማይሰጥ ከለከለን፡፡ ምንም አማራጭ ስናጣ ፒቲኤ (የምሥራቅና

ደቡባዊ አገሮች ልማት ባንክ) ጠየቅን፡፡ ባንኩም ከኬንያና ከሌሎች አገሮች ባለሙያዎች ልኮ እርሻችንን ጐበኙና በጣም

ተገረሙ፡፡ ባንኩ፤ ምንም አላቅማማም፣ ወዲያውኑ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቅዶልን፣ 10 የተለያዩ ከባድ

መሳሪያዎች ገዝቶ ሰጠን፡፡ ከፒቲኤ ተበድረን ተሳክቶልን በመክፈል እኛ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ ነን፡፡ ከዚያ በፊት

ለጫማ ፋብሪካ ሰጥቶ አልተሳካለትም፡፡
አሁንም ላቀድናቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከባንኩ ብድር ለመጠየቅ አሰበናል፡፡ “ግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ ከ20

ሚሊዮን ዶላር በታች አይጠይቀንም፤ እኛም አንሰጥም፡፡ ቶሎ በሉ እንጂ!” እያሉን ነው፡፡ እኛ ከባንኩ ጋር ቤተኛ ነን፡፡

እዚህ አገር ያለ አንድም ባንክ እርሻችንን ጐብኝቶ አያውቅም፡፡ እነሱ ግን ብዙ ጊዜ መጥተው አይተውናል፡፡ እነሱ፣

የእርሻ ችግር ይገባቸዋል፡፡ መጥተው አይተው ችግር ካለብን የግድ ክፈሉ አይሉንም፤ ስታገኙ ትከፍላላችሁ ብለው

ያልፉናል፡፡
መጀመሪያ ሥራ ስትጀምሩ ኢንቨስትመንታችሁ ምን ያህል ነበር?
የመጀመሪያውን 100 ሄክታር ያለማነው በ30 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ አሁን ግን 30 ሚሊዮን ብር ለ1000 ሄክታር ቀርቶ

ለሁለት ሄክታር እንኳ አይበቃም፡፡ ያኔ፣ ጊዜው ጥሩ ስለነበረ፣ ለቀን ሠራተኛ የምንከፍለው 3.50 ነበር፡፡ ዛሬ ግን በቀን

60 እና 70 ብር ነው የሚከፈለው፡፡ የቡና ሥራ ደግሞ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚፈልግ ነው፡፡
ያኔ ምን ያህል ሠራተኛ ነበራችሁ? አሁንስ?
ያኔ 1,500 ያህል ሠራተኞች ነበሩን፡፡ አሁን ቴፒን ጨምሮ ከ20 በላይ ሠራተኞች አሉን፡፡ የቡና ሥራ ወቅታዊ ስለሆነ፣

በለቀማና በእንክብካቤ ጊዜ የጊዜያዊ ሠራተኞች ቁጥር ይጨምራል፡፡ ቋሚ ሠራተኞች ከ6 ሺህ እስከ 7ሺህ ይሆናሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ፣ የገበሬውን ዘመድና ከተለያዩ ዞኖች ሰዎች እናመጣለን፡፡ በትላንትናው ዕለት እንኳ ወደ 2,600

ሰዎች አምጥተዋል፡፡ በዘመቻ የሚሠራው ሁልጊዜ አይደለም፡፡ በሳምንት ሦስት ቀን ሰኞ፣ ረቡዕና ዓርብ ነው፡፡
አሁን ካፒታላችሁ ምን ያህል ነው?
የሁለቱም እርሻ የተለያየ ነው፡፡ የቴፒ ወደ 500 ሚሊየን፣ የመጀመሪያው ደግሞ ወደ 200 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
ስኬታችሁ ያስገኘላችሁ ምን እውቅና አለ?
አዎ! አምና እስካሁን ባለው የእርሻና የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ በደቡብ ክልል በተካሄደው ውድድር፣ እኛ በእርሻ፣

ቢጂአይ ደግሞ በኢንዱስትሪ አሸናፊዎች ነበርን፡፡ ከዚያ በኋላ አምና በባህርዳር ከተማ የገበሬዎች በዓል ነበር፡፡ በዚያ

በዓል ላይ፣ ከገበሬዎች ጋር በመሥራትና በኤክስፖርትና በሌላውም ሁሉ ለውጥ በማምጣት ከመላ ኢትዮጵያ 1ኛ ሆነን

ተሸልመናል፡፡
በዓመት ምን ያህል ቡና ወደ ውጭ ትልካላችሁ?
በእርሻችን የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ስላሉን በኮንስትራክሽን እንሳተፋለን፡፡ ሌላውና ዋነኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ

ለሙከራ በ200 ሄክታር መሬት ላይ የተተከለ ብቸኛ የፓልም ኦይል ተክል አለን፡፡ ቴፒ እርሻው ላይ የተተከለ መጠነኛ

የዘይት ፋብሪካም አለን፡፡፡ ፓልም ላይ ኢንቨስት ወይም ጥናት አደርጋለሁ የሚል ሰው እኛ ጋ ነው የሚመጣው፡፡
ሌላ ደግሞ የንብ እርባታ አለን፡፡ እርሻው ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ቀፎዎች አሉን፡፡ ከአሁን በፊት ሁለት ጊዜ ማር

ኤክስፖርት አድርገናል፡፡ አሁን ምርቱን ለመጨመርና በብዛት ወደ ውጭ ለመላክ ፋብሪካ እየተከልን ነው፡፡
ቅመማ ቅመም ደግሞ ከ500 እስከ 600 ሄክታር የሚሆን እርሻ አለ፡፡ ሄል፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ዝንጅብል፣ ኮረሪማ፣ …

እናመርታለን፡፡ ካሁን በፊት ሁለት ጊዜ ኤክስፖርት አድርገናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከውጪው ገበያ የአገር ውስጥ ዋጋ

ስለሚበልጥ እዚሁ ጨረታ አውጥተን እንሸጣለን፡፡
200 ሄክታር የአትክልት እርሻም አለን፡፡ ማንጐ፣ ብርቱካን፣ አቡካዶ፣ ሙዝ፣ … አለን፡፡ እነዚህም እዚሁ በሚሊዮን

ብሮች ይሸጣሉ፡፡ ለሠራተኛው በቆሎ ይዘራል፣ ወፍጮ ቤቶች፣ ዳቦ ቤቶች፣ … በቡና ለቀማ ጊዜ ለሠራተኛው

የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ አለ፡፡
እዚህ ይህ ማሽን ምንድነው የሚሠራው?
ይኼ ማሽን ፒቲኤ ባንክ በ1.1 ሚሊዮን ዩሮ ከጀርመን የገዛልን እጅግ ዘመናዊ የቡና ፕሮሰስ ማድረጊያ መሳሪያ ነው፡፡

መሳሪያው፣ ድምፅ የለው፣ አቧራ የለው፣ ብናኝ የለው፣ አስፈላጊ ሲሆን ጣሪያው ተከፋች ነው፤ በአጠቃላይ ሙቀትና

ቅዝቃዜ መቆጣጠሪያና አቧራ መምጠጫ አለው፡፡
ሁለት ዓይነት ቡና ነው ወደዚህ የሚመጣው፤ የታጠበና ያልታጠበ ይባላል፡፡ የታጠበ የሚባለው፣ የበሰለው ቀይ የቡና

ፍሬ ተለቅሞ፣ በወፍጮ ተፈልፍሎ፣ታጥቦና ደርቆ ከነገለባው ይመጣል፡፡ ያ ቡና እዚህ ማሽን ውስጥ ገብቶ ሲፈለፈል

ቡናው ከገለባው ይለያል፡፡ ያ ቡና እንግዲህ የተሰባበረና፣ አፈርና ቆሻሻው ተለቅሞ፣ ተመዝኖ ኤክስፖርት ይደረጋል፡፡

ያልታጠበው ቡና፣ እዚያው ከነልባሱ (ጀንፈል) ደርቆ፣ በደረቅ የቡና ወፍጮ ተፈልፍሎ መጥቶ የታጠበው ቡና

በሚያልፍበት ሂደት ያልፋል፡፡
እዚህ ስንት ሠራተኛ አላችሁ?
በአንድ ፈረቃ 300 ሠራተኞች አሉ፡፡ ሚያዝያና መጋቢት ሥራ ስለሚበዛ በሦስት ፈረቃ ስንሠራ ቡና ለቃሚ ሴቶች

900፣ ካቦ ጫኝና አውራጅ፣ … ሲደመሩ፣ ከ1000 በላይ ሠራተኞች ይኖሩናል። በሁለት ፈረቃ ከሆነ ደግሞ 600

ሠራተኞች ይኖራሉ፡፡ ከዚያ በታች ግን አይወርድም፡፡
ቡናውን ከእርሻ ወደዚህ የምታመጡት በኪራይ መኪና ነው?
አይደለም፤ በራሳችን መኪኖች ነው፡፡ 10 ከባድ መኪኖች ስላሉን በእነሱ እናመጣለን፡፡ ከዚህ ደግሞ ሲሚንቶ፣ ማዳበሪያ፣

ኬሚካል፣ የሠራተኞች የሥራ ልብስ፣ … ጭነው ይመለሳሉ፡፡ ወደ ጅቡቲ የምንልከው ግን በድርጅቶች መኪና ነው፡፡

ሥራ በሚበዛበት ጊዜ መኪኖች ስለማይገኙ መዘግየት ይፈጠራል፡፡ ያንን ክፍተት ለመሙላት የራሳችን መኪኖች

እንዲኖረን እያሰብን ነው፡፡
ለመንግሥት ግብርና ታክስ በዓመት ስንት ትከፍላላችሁ?
የቴፒ እርሻ ገና ነው፡፡ በበፊተኞቹ ግን በአጠቃላይ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ብር እንከፍላለን፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ ያጋጠማችሁ ትልቅ ፈተና ምንድነው?
እኛ አገር ያለው ፈተና ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው፣ እንደ ዘንድሮ የቡና ዋጋ በጣም ወድቆ አያውቅም፡፡
በዛሬው ቀን (ባለፈው ረቡዕ) በኒውዮርክ ገበያ አንድ ፓውንድ 1.05 ዶላር ነው። (አንድ ኪሎ 2.2 ፓውንድ ነው) አምና

በዚህ ጊዜ ቡና በጣም ወድቋል በተባለበት ጊዜ፣ አንድ ፓውንድ ቡና 1.50 ዶላር ነበር፡፡ ከዚያ በፊት 2.20 እና 2.50

ዶላር ነበር፡፡ ከፍተኛው 3.50 ዶላር ነበር። ቡና እጅግ ለመውደቁ በ3.50 እና በ1.05 መካከል ያለውን ልዩነት ማየት

ይበቃል፡፡ አምና በጣም ሞተ እያልን 1.50 ነበር፤ ዘንድሮ 1.05 ዶላር።
በውጭ የቡና ዋጋ በጣም ቀንሶ እዚህ የቡና ለቃሚዎች ዋጋ ጨምሯል፡፡ በፊት ለአንድ ኪሎ ቡና ለቀማ 0.50ሳ. ነበር

የምንከፍለው፡፡ አሁን በኪሎ እስከ 2 ብር እንከፍላለን፡፡ አንድ ኪሎ ንፁህ ቡና ለማግኘት 6 ኪሎ እሸት ቡና መለቀም

አለበት። የሠራተኛ ጉልበት፣ 3ብር፣ 5ብር፣ 10፣15፣ … እያለ አሁን በቀን 70 እና 80 ብር ደርሷል፡፡ የዓለም የቡና ዋጋ

ግን እጅግ አሽቆልቁሏል፡፡ በቡና ንግድ የተሰማሩ ሁሉ ኪሳራ ላይ ናቸው፡፡ አምና፣ ዘንድሮ ይሻለዋል ብለን በተስፋ

ጠብቀን ነበር፤ ከአምናው የበለጠ ሞተ፡፡
 አሁንም በሚመጣው ዓመት የተሻለ ይሆናል ብለን በተስፋ መጠበቅ ነው፡፡ ሊሻልም ሊብስም ይችላል፡፡ የቡና ገበሬ

ሕይወት ይኼ ነው - በተስፋ መኖር፡፡
የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?
የማር ፋብሪካ አቋቁመን ማር አሽገን ለመላክ ከሁለት ኩባንያዎች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ (ሮስትድ ኮፊ) ለማቅረብ፣

ጥናቱን ጨርሰናል፤ ይህ ሥራ ከባድ ነው፡፡ እንዲሁ ዘለህ የምትገባበት አይደለም-አደጋ አለው፡፡ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር

እየተነጋገርን ነው፡፡ ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት ይሳካል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
ከአገር ውስጥ ባንኮች እስካሁን ምንም አልወሰዳችሁም?
አይ! አሁን ለቡና ለቀማ ከአዋሽ ኢንተርናሽናልና ከዳሽን ባንክ ጋር እየሠራን ነው፡፡ ከእነዚህ በስተቀር ከሌሎች ባንኮች

ጋር አልሠራንም፡፡ እስካሁን በራሳችን ገንዘብ ነው ስንሠራ የነበረው፡፡
አቶ ታደለ አብረሃ ባለ ትዳርና የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ልጆቹ እየተማሩ ናቸው፡፡ የትልቁ ልጅ ዕድሜ 14 ዓመት

ሲሆን ትንሿ ሴት ልጅ ደግሞ ስምንት ዓመቷ ነው፡፡

Saturday, 30 November 2013 11:18

መነሻ ስዕል

አያልቅም ይህ ጉዞ…
ማስመሰል - መተርጐም
በቀለም መዋኘት
ከብርሃን መጋጨት
ለማወቅ ለመፍጠር ባዶ ቦታ መግባት፡፡
መፈለግ… መፈለግ
አዲስ ነገር መፍጠር
ከማይታየው ጋር ሄዶ መነጋገር፡፡
ህይወትን መጠየቅ
ሃሳብን መጠየቅ
መሄድ መሄድ መሄድ…
ከጨረቃ በላይ
ከኮኮቦች በላይ
ከሰማዩ በላይ፡፡
መጓዝ ወደ ሌላ - ባዶ ቦታ መግባት፡፡
በሃሳብ መደበቅ
መፈለግ ማስገኘት፡፡
አያልቅም ይህ ጉዞ…

Published in የግጥም ጥግ

“አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከሁለቱም ታናሹ አባቱን … ‘አባቴ ሆይ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ’

አለው፡፡’ ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፣ ከዚያም

እያባከነ ገንዘቡን በተነ፡፡ ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፣ እርሱም ይጨነቅ ጀመረ፡፡ ሄዶም ከዚያች

አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፣ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው፡፡ እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ

ይመኝ ነበር፣ የሚሰጠውም አልነበረም፡፡
ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፡- … ‘ተነስቼ ወደ አባቴ እሄዳለሁና … አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልሁ …

ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ’፡፡ ተነስቶም ወደ አባቱ መጣ…”
የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15፣ ቁጥር 11-19
*   *   *
ሚያዝያ 3 ቀን 1963 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ላይ እንዲህ የሚል ዘገባ ወጥቶ ነበር፡፡ “The Saudi

press (government) is preoccupied with trying to payback this country’s hospitality with

hostility” (በአሁኑ ሰዓት የሳዑዲ መገናኛ ብዙሃን የዚህችን አገር (የኢትዮጵያን) እንግዳ (ስደተኛ) ተቀባይነት ውለታ

በአሳዳጅነት ለመክፈል እየዳከረ ነው) ይላል፡፡
አዎ…! ሰሞኑን የሳዑዲ መንግስትና ህዝብ በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ላይ እያደረሰ ባለው አረመኔአዊ ድርጊት ልቡ

ያልቆሰለና ያላመረቀዘ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊም መካና መዲና ከሚጠሩባት ቅድስት ምድርና

ህዝብ ይህ መሰማቱ አስገራሚና አዲስ ክስተት ሆኖበታል፡፡ ጥያቄው ግን እውነት ይህ ድርጊት አዲስ ክስተት ነው ወይ…?

የሚል መሆን አለበት፡፡
ብዙ የታሪክ ድርሳናት እንደሚመሰክሩት የሳዑዲ አረቢያ ታሪክ፣ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲ ወዘተ… በተለይ ደግሞ

ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያላት አመለካከት ከፍጥረቱ አንስቶ በሃጢአት፣ በክፋት፣ በምቀኝነትና በመሰሪ ድሮች

የተተበተበ ነው፡፡ የዚህ እውነት ጠቅላይ ማረጋገጫው ደግሞ ከአለም ህዝብ ሁሉ በተለየ ነቢዩ መሃመድ (ሰ.ዐ.ወ)

…‘ኢትዮጵያውያንን አትንኳቸው…’ ብለው የሰጡትን ዘላለማዊ ትዕዛዝ እያወቁ ገድፈው በስደት ምድራቸው ላይ ያሉትን

የጊዜ ስደተኞች ዜጎቻችንን ደም ማፍሰሳቸው ነው። ይህ የታሪክ ጉንጉናቸው ሲዘረዘር ደግሞ እንዲህ ነው፡፡
የሃርቫርዱ ፕሮፌሰር ፋሪድ ዘካሪያ The Future of Freedom በሚል መፅሃፉ ላይ የአንድ አገር ሃብት (ንዋይ) በሁለት

መንገድ ይገለፃል ይላል፡፡ አንደኛውና ጤነኛው፤  በላብ እና በልፋት በጊዜ ሂደት ውስጥ የሚገኘው ሃብት (Earned

Wealth) የሚባለው ነው፡፡ ለዚህም ከድህነት ተነስተውና በዘመናት የእድገት ትግል ጎዳና አልፈው ዛሬ ሃብታም

የሚባሉትን አገራት ልብ ይሏል፡፡
ሁለተኛውና ያበደ ውሻ የሚያደርገው ሃብት ደግሞ በከፋ ድህነትና ስንፍና ውስጥ እየኖሩ አንድ ማለዳ ላይ እንደ

እሳተ-ጎሞራ ፈንድቶና ተትረፍርፎ ደጅ ላይ የሚገኘው ሃብት (Explored wealth) የሚባለው ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ

የሁሉም ማለት በሚያስዳዳ መልኩ፣ ሃብታቸው በነዳጅና ማዕድን ፍንዳታ ላይ የተመሰረተውን አብዛኛውን አረብ

አገራትን ልብ ይሏል፡፡ ከነዚህ መካከል አንዷ ሳዑዱ አረቢያ ናት፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ዛሬ ጎራዴዋን መዝዛ የወንድምና እህቶቻችንን አንገት በገሃድ ስትቀላ የዚህ ታሪካዊ ዕብደት መስካሪ

ትውልድ ሆንን እንጂ፣ የነቢዩን ስደተኞች ከመቀበልና በነፃነት እምነታቸውን እንዲያራምዱ ከማድረጓ አንስቶ፣

እስከዛሬው ድረስ ለዋለችላት ውለታ ኢትዮጵያ በሳዑዲ የደረሰባት ግፍ፣ በደልና ክህደት እንዲህ ተብሎ በአጭሩ ተገልፆ

የሚያልቅ አይደለም፡፡
ሳዑዲ …ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ለመውጋት በመጣ ጊዜ በኢትዮጵያ ተራራና ኮረብታዎች፣ እንዲሁም በቆላው ምድረ በዳ

መድፍና ጥይቱን እንዲያጓጉዝ ዕልፍ ግመሎችን ለጣሊያን በርካሽ ስትሸጥ፣ ጣሊያን ለ5 ዓመታት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ

ጀርባዋን የሰጠች ቀዳሚ አገር ስትሆን፣ ከወረራው በኋላ ከፍልስጤም፣ ከሊቢያና ከሩስያ ጋር በማበር ኢትዮጵያን

ለማፈራረስ ለዚያድባሬው ሶማሊያና ለኤርትራው ነፃ አውጪ ተገንጣይ ጦር በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ድጋፍ

ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሰላማዊውን ኢትዮጵያዊ ሙስሊምና ክርስቲያን በሃይማኖት ሽፋን

ፍቅራቸውን ለማጥፋትና ደም ለማቃባት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተኝታ የማታውቅ መሆኗ ሳያንስ፣ ሰሞኑን ደግሞ

የዜጎቻችንን ደም በምድሯ ማፍሰስ ጀመረች፡፡ ይህንንም ከታሪኳ ስረ መሰረት ጀምረን አለፍ አለፍ እያልን በተለይ

በኢትዮጵያ አንፃር እንመልከት፡፡
“በ1974 አንድ የሳዑዲ ዲፕሎማት በአንድ ወቅት ሪያድ ውስጥ በትልቅ የመንግስት ህንፃ አጠገብ ያለ የቆሻሻ ክምር ላይ

የሚርመሰመሱ ፍየሎች ፎቶ አሳየኝ። ምን እንደሆነ ስጠይቀው ‘ፍየሎቹ የሳዑዲ አረቢያ ዋነኛ የቆሻሻ ማስወገጃ መንገድ

ናቸው’ አለኝ” … ይላል ጆን ፐርኪንስ የተባለው አሜሪካዊ የኢኮኖሚ ጦረኛ confessions of an economic hit man

በተባለ መጽሐፉ ላይ፡፡ ታዲያ ሳዑዲ አረቢያ ከዚህ አሳፋሪ ድህነትና ቆሻሻ ተነስታ ዛሬ የደሃ አገራት ዜጎች መሰደጃ፣

ሃብታምና ውብ የሆነችው እንዴት ነው…?  
በ18ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሞሃመድ ኢብን ሳዑድ የተባለ አንድ ጦረኛ፤ ከወግ አጥባቂ ዋሂቢ ፅንፈኞች ጋር በመቀላቀል

በጣም ሃያል የሆነ ግንባር ፈጥሮ የኢስላም ቅድስት ከተሞች የሆኑትን መካና መዲናን ጨምሮ አብዛኛውን የአረብ

ፔኒንሱላ ድል መቶ መግዛት ጀመረ። ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ጦርነት በከፈተች ጊዜ ለሞሶሎኒ ግመል ሲሸጥ

ከርሞ፣ ሞሃመድ ኢብን ሳዑድ በ1955 አርጅቶ ከመሞቱ ከሁለት ዓመት በፊት በ1953 ሳዑድ የተባለውን ልጁን አነገሰ፡፡

ንጉስ ሳዑድ በተፈጥሮው የአባቱን ያክል ሃይለኛ ያልነበረና ብዙም ሸር ያልበዛበት ለዘብተኛ ቢሆንም ቅሉ፣ እርሱም

በ1964 ለሁለት ዓመታት ጠ/ሚኒስትሩ በነበረው በገዛ ወንድሙ በልዑል ፋይሰል ስልጣኑን ተነጠቀ፡፡
እንግዲህ ልዑል ፋይሰልም ንጉስ ከሆነ በኋላ ኢትዮጵያን የሚወር ጣሊያን ባለመኖሩ ግመል ባይቸብችብምና ለኢትዮጵያ

ጠላቶች ስትራቴጂካዊ የአየር ሃይል ጣቢያ ባያዘጋጅም፣ እሱም እንደ አባቱ የነቢዩን መልዕክተኞችና ስደተኞች “ቤት

(አገር) የፈጣሪ ነው” ብላ በሁለት እጆቿ የተቀበለችውን ኢትዮጵያን በሌላ መልክ ማጥቃት ያዘ፡፡ ነገሩም በአጭሩ እንዲህ

ነው:-
በ1960 እዚሁ አዲስ አበባ ላይ በአፄ ሃይለ ስላሴ ላይ ተቃጥቶ የነበረውን መፈንቅለ መንግስት በማክሸፍ ሚና ውስጥ

ጉልህ እጅ የነበራት እስራኤል በሰራችው ውለታ ሰበብ ከንጉሱ ጋር ወዳጅነቷን አጠነከረች፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም

የእስራኤልን ሃይማኖታዊ ዳራ፣ ሃይማኖታዊ መሰረት ከነበረው አገዛዛቸው ጋር የበለጠ በማቀራረብ፣ ከእስራኤል ጋር

ያላቸውን ግንኙነት ከፖለቲካዊ ውለታ ባሻገር ‘ሰማያዊ’ ማድረጋቸውን ተከትሎ በወቅቱ በተለይ በአረብ አገራት ሲጠላና

ሲወገዝ የነበረው “ክርስትያናዊ-ፅዮናዊነት” (Christian-Zionism) በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል መጠናከር ጀምሮ

ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን የሳዑዲው ንጉስ ፋይሰል የኢትዮጵያንና የእስራኤልን ግንኙነት በተመለከተ ከሁለት ዋነኛ ነገሮች

አንዱን መምረጥ ነበረበት፡-
በኢትዮጵያ ላይ ስር እየሰደደ የነበረውን የእስራኤልን ፅዮናዊነት መቃወምና ብሎም ማጥፋት ወይም
በአረብ አገራት ላይ እየገነነ የመጣውንና ስጋት ላይ የጣለውን የግብፁን ንጉስ ናስርን ከእስራኤልና ኢትዮጵያ ጋር በማበር

መጣል (ማዳከም)
ፋይሰል ፍጥረተ ተኩላነቱን ተጠቅሞና ለምድ ለብሶ ከኢትዮጵያና ከእስራኤል፤ ጋር በማበር በግብፅ ላይ የዘመተውን

የየመንን ጦር በሁሉም መልኩ፤ ከገንዘብ እስከ ጦር መሳሪያ፣ ከጦር አውሮፕላን እስከ ሰለላ መገናኛ ድረስ በማቅረብ

ይረዳ ጀመረ፡፡
በዚህ ሁኔታ ግብፅም ከተዳከመች በኋላ በሰኔ 1967 እስራኤል በግብፅ፣ ሶሪያ እና ዮርዳኖስ ላይ ድል በመንሳት ምስራቃዊ

ኢየሩሳሌምንና ከፊል የሲናይ በረሃን ተቆጣጠረች፡፡ ወዲያውም ተሸናፊዎቹ ‘አንድነት በሽንፈት’ (Unity in Defeat)

በሚል መሪ ቃል ተዋህደው ሲለማመጡት የነበረውና፣ በነዳጅ ሽያጭ የሃብት ተራራውን እየቆለለ ብዙም ጆሮ ያልሰጠው

የሳዑዲው ፋይሰል በመጨረሻ በ1970 የግብፁ ናስር ሲሞትለት ማህበሩን ተቀላቀለ፡፡ አጀንዳውም “በእስራኤል

የተያዘውን ምስራቅ ኢየሩሳሌም ማስመለስ ማለት የኢስላምን ቅድስት ቦታ ማስመለስ” የሚል ሆነ፡፡ ወዲያውም በሳዑዲ

ረዳትነት ግብፅ ናስርን በተካው አንዋር ሳዳት አማካኝነት ጥቅምት 6 ቀን 1973 ያልታሰበ ጦርነት እስራኤል ላይ

ከፈተች፡፡ ከአስር ቀናት በኋላ ደግሞ በቀዳሚነት የእስራኤል አጋር በነበረችው አሜሪካን ላይ ያነጣጠረ አስደንጋጭ

የነዳጅ የ70% ዋጋ ጭማሪ (The Oil Embargo) ተከተለ፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ፣ በተለይ የአሜሪካ በ1929 ከነበረው

ባልተናነሰ መልኩ ተናጋ፡፡ እስራኤል ላይ ጦርነት ከመከፈቱ በፊት ንጉስ ፋይሰል ለቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ አንድ

መደራደሪያ አሳብ አቀረበ፡-
“… በጦር፣ በኢንተለጀንስ እና በሌሎች ስራዎች ኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ኢንቨስትመንት የነበራትን እስራኤልን ከኢትዮጵያ

እንዲያስወጡና በምትኩ ኢትዮጵያ ከእስራኤል የምታጣውን ድጋፍ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ የ200 ሚሊዮን ዶላር ስጦታ

…’
በዚህ ወቅት ራስ አስራተ ካሣ እስራኤልን በመወገን አሳቡን ሲቃወሙ፣ ጠ/ሚ አክሊሉ ሃብተወልድ ደግሞ የእስራኤል

ወዳጅነት ከጥቅሙ ይልቅ ከአረብ መንግስታት ጋር ሊፈጥር የሚችለውን ችግር በመተንበይ ተቃርነው የነበረ ቢሆንም

ንጉሠ ነገሥቱ ለውሳኔ ሲዋልሉና ንጉስ ፋይሰልን በተለያየ ሽፋን ሲደልሉ ሳለ ነበር ጦርነቱ በእስራኤል ላይ ተከፍቶ

በመጨረሻ እጅ የሰጡት፡፡ ሂደቱም በጊዜ ሰሌዳ እንዲህ ነበር ይላል የቴላቪቩ ፕሮፌሰር ሃጌ ኤርሊች Saudi Arabia &

Ethiopian: Christianity and politics በሚለው መፅሃፉ ላይ፡፡
ጥቅምት 19፣ 1973፡- “እስራኤላውያንን የማስወጣት እርምጃህ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እኔና አንተ የምናወራው

ነገር የለም፡፡ ይልቅስ ማድረግ ያለብህን አድርግ እንጂ ወሬህን ተው…” ብሎ ንጉሱ ፋይሰል ለኃይለስላሴ ቴሌግራም

ላከ፡፡
በአራተኛው ቀን ጥቅምት 23፣ 1973፡- ንጉሠ ነገሥት ሃይለ ስላሴ 100 የሚጠጉትን እስራኤላውያንን ከአገር ማስወጣት

ጀምረው፤ ህዳር 3፣ 1973 የመጨረሻውን ሰው አምባሰደር አይነርን በማሰናበት አጠናቀቁ፡፡ የዚያኑ ቀን ንጉስ ፋይሰል

ለኃይለ ስላሴ ቴሌግራም ሰደደ፡- “አለምን ለመቆጣጠር ትልቅ ህልም የነበረውን ፅዮናዊነትህን በማስወገድህ እንኳን ደስ

ያለን” የሚልና ቃል ከተገባው ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሣ እንደሚያደርግ የሚያረጋግጥ፡፡ ከዚያስ …?
ይህ በሆነ በ3 ወር ገደማ ንጉሠ ነገሥት ኃይለስላሴ በጥር 22፣ 1974 ከሮም መልስ ከራስ አስራት ካሣ ጋር በመሆን

ትልቅ አቁፋዳ ይዘው ወደ ጅዳ እንግድነት ጎራ ቢሉም ቅሉ ‘የውሾን ነገር ያነሳ …’ እንዲሉ የ200 ሚሊዮን ዶላሩ ጉዳይ

ሳይነሳ ቀረ፡፡
“በምትኩ ንጉሰ ፋይሰል የ35 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ ብቻ እንደሚሰጣቸውና እርሱም አብዛኛው የሚውለው ‘ለእስልምና

ተቋማት መገንቢያ’ እንደሆነ ሰምተው ሲመለሱ እጅግ ከማዘናቸው የተነሳ በመናገሻቸው ለቀናት ራሳቸውን አግልለው

በብስጭት ነበር የከረሙት” ይላሉ የራስ አስራተ ካሣ ልጅ አባታቸው እንዳጫወቷቸው፡፡ በኢትዮጵያ አንፃር ይህ እንዲህ

ሳለና፣ እስከ ህዳር 1974 ለአምስት ወራት ብቻ የቆየ አለም አቀፋዊ ወሳኝ ኢኮኖሚያዊ ኃያልነቷን ብታሳይም ቅሉ ዓመት

ባልሞላው ጊዜ እጅግ በረከሰና ስጋዊ ዝሙት በተቀላቀለበት ውርደት ሳዑዲ እጇን ለአሜሪካ ሰጠች። እንዴት…?
*   *   *
በ1975 አሜሪካ MAIN በተባለው ኮርፖሬት ድርጅት አማካኝነት ሳዑዲ አረቢያን ‘ሃብታምና በጣም ዘመናዊ’ ሊያደርግ

የሚችል፣ በተቃራኒው ደግሞ ‘የሳዑዲን ነዳጅና በዋጋ ላይ ያላትን ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ የሚያሳጣት’ ዕቅድ ነደፈችና

በኢኮኖሚው ጦረኛ ጆን ፐርኪንስ በኩል ዕቅዱን ለንጉሱ አቀረበች። ንጉሱና አጋሮቹ በሂደት እጅ ሰጥተው ቢስማሙም

ልዑል W. የተባለው ወሳኝ ልጅ ግን “በኢስላም ላይ ከመስቀል ጦርነት ያልተናነሰ ጥቃት ነው” በሚል በመቃወሙ ትልቅ

ችግር ተፈጠረ፡፡ ሆኖም በልዑሉ ላይ አንድ ሚስጥር በመገኘቱ ብዙም ሳይቆይ መላ ተገኘ፡፡ ለካንስ በጨዋታቸው መሃል

ልዑሉ ‘ብሎንድ’ ተብለው የሚጠሩትን የምዕራብ ቆነጃጅት ሴቶችን እንደሚወድ ተሳብቆበት ኖሮ፣ በጉዳዩ ላይ ቀጣይ

ስብሰባዎችና ድርድሮች ለማድረግ ልዑሉና የሳዑዲ ልዑካን ወደ አሜሪካ ሲሄድ ‘ሳሊ’ (Sally) የምትባል ቆንጆ ብሎንድ

ተዘጋጀችለት፡፡
ሳሊ በአሜሪካ የአንድ የዩናይትድ ኤርላይንስ ፓይለት ሚስት በመሆኗና ባሏ ለረጅም ቀናት በጉዞ ምክንያት አብሯት

ባለመሆኑ ከሌሎች ሴቶች ጋር እንደሚማግጥ የሰማችና በቀል ያረገዘች ብትሆንም፣ ‘ይህ ታላቅ አገራዊ ጉዳይ (ውለታ)

ነው’ በሚል መንግስታዊ ጫና ተስማምታ ስታበቃ ‘ታጥባና ታጥና’ ለልዑሉ ቀረበችለት፡፡ ልዑሉም ነፍስያው

እስክትጠግብ ድረስ ሲደሰትባት ጊዜ የመስቀል ጦርነቱን ገድፎ በአቡነ ሄነሪ ኪሲንጀር የተዘረጋለትን የኢኮኖሚ መስቀል

ተሳልሞ ሲያበቃ፣ ስምምነቱን በመፈረም ተጠመቀ፡፡ ወደ አገሩም ሲመለስ ደግሞ ሳሊን ማስከተል ስላልተቻለ ሌላ ሳሊ

ተፈልጋ ተመረቀችለት፡፡
አሜሪካም ዳጎስ ያለ ወለድ ብድር ሳዑዲ አረቢያንን ከመሰረቱ ጀምራ ከተሞቿን በማስተር ፕላን፣ ፋብሪካዎቿንና ታላላቅ

የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማቶቿን ደግሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ገነባች፡፡ ሳዑዲም ለአመታት በነዳጅ ዋጋ ላይ እጇን ተቆርጣ፣

በአንድ በኩል መሰረታዊ ዕዳዋን በነዳጅ ለአሜሪካ እየከፈለች፣ አሜሪካም በየቀኑ በሚቆርጥላት ወለድ በሳዑዲ ያሉትን

ኮርፖሬት ድርጅቶቿን እየደጎመች፣ ከ1975 ጀምሮ “በዝሙት ዳኝነት” የነዳጅ ዋጋ ተጠቂ ሳትሆንና፣ ሳዑዲን ከOPEC

ጥዋ አስፈንግጣ በሰላም መኖር ጀመረች፡፡
እንግዲህ አጠር ባለ መልኩ በዚህ መሰረት እዚህ የደረሰች ሳዑዲ አረቢያ የተባለች አገር ናት የዚችን ቅድስት አገር

ውልዶች ደም ታፈስስ የያዘችው፡፡ አዎ ዛሬ ዛሬ በመካከለኛው ምስራቅ በየደቂቃው እየተቀጣጠለ የምናየው ቀውስና

ጦርነት መሰረቱ አንድም እንደ እሳተ ጎሞራ በሆነ ወቅት በፈነዳው የነዳጅ ሃብት (Petro-dollar) አማካኝነት፣ ሁለትም

በሃይማኖት በተሸፈነ መሰረታዊ የማንነት ችግር ነው፡፡ እነዚህ መሰረታዊ ችግሮች ‘በእውቀት ማነስ’ ሲታሹ ደግሞ

ውጤቱ የከፋ ሆነ፡፡ ገንዘቡ ሲገኝ በራስ ወዳድነት፣ የአጠቃቀም ብልሃትና እውቀት በማጣትና፣ በካበተው ገንዘብ ስካርና

ዕብደት ሰበብ ደግሞ ቅዱሱን የሃይማኖቱን መመሪያ በብዙ የተሳሳቱ ትርጓሜዎች በማላሸቃቸው፣ ዛሬ መካከለኛው

ምስራቅ ብቻ ሳይሆን ዓለም በመላው እየታመሰችበት ትገኛለች፡፡ ይህም ሲባል ግን ‘ስር ነቀሉ የምዕራባዊያን መሰሪ

የውስጥ ለውስጥ መርዛማ መርፌ’ የአደባባይ ምስጢር እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡
*   *   *
ዋናው ጉዳያችን ወደ ሆነው የዜጎቻችን ደም መፍሰስ ስንመጣ ግን ‘ይህ ሁሉ እንዳይፈጠርም ሆነ ከተፈጠረ በኋላ የኛስ

መንግስት ምን አደረገ…? መጀመሪያውኑስ ከነዚህ አገራት ጋር ሊኖር የሚገባው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ምን መሆን

እንደነበረበት ከፖለቲካዊ ጥቅም ባሻገር ማህበራዊውን እና ታሪካዊውን ገፅታ ተመልክቶታል ወይ…? ኢትዮጵያውያን

እንዲወጡ ትዕዛዝ ከተላለፈበት ወቅት ጀምሮ፣ እንኳንና መወሰድ የነበረበትን እርምጃ ተግባራዊ አድርጎ ለህዝብ ሂደቱን

በየጊዜው ማሳወቅ ይቅርና መጀመሪያውኑስ ቢሆን ለዜጎች ተቆርቁሯል ወይ…?’ ብለን መጠየቅ ይገባል፡፡
ይህ ክስተት የኢትዮጵያ መንግስት በሳዑዲ የሚገኙት ዜጎቹ ‘ህገ-ወጥ’ ተብለው ስም ስለተሰጣቸው ብቻ፣ በቃልም ይሆን

ከቃል በላይ ደግሞ በተግባር ‘በህገ-ወጦች ላይ ምንም አያገባኝም’ የሚል አቋም መያዙን ያረጋገጠ ተግባር መሆኑን

የመሰከረ ነው፡፡ ዳሩ ‘ለህጋውያንስ ቢሆን ምን ተደርጎ ያውቃል…?’የሚል ጥያቄ ቢነሳ ስንት ህጋዊ ዜጎች ደመ-ከልብ

ሆነው እንደቀሩ ቤት ይቁጠረው፡፡
መግቢያችን ላይ በጀመርነው ወንጌል ላይ … ሰነፉ ልጅ ገንዘቡና ጨርሶን ተሰቃይቶ ወደ አባቱ ተመለስ ይላል፡፡ ከዚያስ

…?
“አባቱም ገና ሩቅ ሳለ አየውና አዘነለት፣ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው፡፡ … አባቱም ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለውን

ልብስ አምጡና አልብሱት፣ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፣ የሰባውን ፋሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፣ እንብላም ደስም

ይበለን፣ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ህያው ሆኗል፣ ጠፍቶም ነበር ተገኝቷል …
ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበርና መጥቶም … ተቆጣ፤ ሊገባም አልወደደም…፡፡ አባቱንም …‘እነሆ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ

ተገዝቼልሃለሁ…፣ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጠቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፡፡ ነገር ግን ገንዘብህን

ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት’ አለው፡፡
እርሱ ግን፣ ‘ልጄ ሆይ አንተ ሁልጊዜው ከእኔ ጋር ነህ፣ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፡፡’ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ

ነበረ-ሕያው ስለሆነ፣ ጠፍቶም ነበረ-ስለተገኘ፣ ደስ እንዲለን ፍስሐም እንድናደርግ ይገባናል’ አለው፡፡”
ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15፣ ቁጥር 20-32
አዎ…! እንኳንና ኢትዮጵያዊ፣ ማንኛውም መንግስት ስለ ዜጐቹ ልክ እንደዚህ አባት ሊሰማው ይገባል፡፡ ዜጎች ኢትዮጵያዊ

ሆነው ሳለ በህገ-ወጥ መንገድ ቀርቶ ህጋዊም በሆነ መንገድ አገራቸውን ትተው መሰደዳቸው ተገቢ አይደለም፡፡ ተገቢ

አይደለም ሲባል ግን ጥቃት በደረሰባቸው ጊዜ ሊካዱ ይገባል ማለት አይደለም። እንኳንና ለመመለስ እየፈለጉ መንገዱን

ተከልክለው ቀርቶ፣ የመመለስ አሳብ ባይኖራቸውም፣ ገና ለገና ‘እኔ ሳላውቀውና ሳልባርካቸው ስለሄዱ አያገባኝም በሚል

አንድምታ ጆሮ ዳባ ማለት ‘ሕዝባዊ ነኝ’ ከሚል መንግስት የሚጠበቅ አይደለም፡፡
ይልቅንስ በፅኑ እንቅልፍ ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት፣ በባዕድ አገር በግፍ የምትፈስ አንዲት ጠብታ ደም፣ እዚህ

ኢትዮጵያ ላይ የምትነዝራቸውና የምትወጥራቸው ብዙ የደም ስሮች እንዳሉ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የደም ስሩ ሲጎተት

ደግሞ፣ እንኳንና በቁሙ ያለ የሞተውም ቢሆን በሃያል በቁጣ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ይህ ነው የኢትዮጵያ ስረ-መሰረታዊ

ትርጓሜ፣ ይህ ነው የኢትዮጵያውያን የደም አይነት፡፡ ምክንያቱም የዓለም ታሪክ እንደሚመሰክረው፣ የኢትዮጵያዊ ደም

በባዕድ አገር ፈሶ የሚያውቀው ለባዕዳኑ ነፃነት መስዋዕት ሲሆን እንጂ፣ ጠያቂና ባለቤት-አልባ ከንቱ ደም ሆኖ

አይደለምና፡፡
ሰላም…!

Published in ህብረተሰብ
Page 2 of 19