አብዛኛው ሙዚቃ አፍቃሪ የሚያውቀውና ዝነኝነት የተቀዳጀበት ዘፈኑ “ሰላ በይልኝ” የሚለው ቢሆንም በኢትዮጵያ ያልተለቀቁ በርካታ ዘፈኖች ያህል እንዳሉት ይናገራል - ወጣት ድምፃዊ ጐሳዬ ቀለሙ (ጃኪ ጎሲ)፡፡ ወደ ሙዚቃው ህይወት የገባው ገና በ13 ዓመቱ ነበር - በትያትር በኩል፡፡ በታዳጊነቱ ከታዋቂ አርቲስቶች ጋር ትያትር ለማሳየት ወደ ፈረንሳይ ሄዶ ለበርካታ ዓመታት ወደ አገሩ አልተመለሰም፡፡ በጀርመን በሬጌ ባንድ ውስጥ እንግሊዝኛ ዘፈኖችን ሲያቀነቅን የቆየው ጃኪ ጐሲ፤ የመጀመርያ የአማርኛ ነጠላ ዜማውን ኢትዮጵያ መጥቶ እንደሰራ ይናገራል፡፡ ባህላዊ ዘፈኖችን እያዘመነ በመስራት ወጣቱ ባህላዊውን ሙዚቃ እንዲወደው የማድረግ ፍላጐት አለው፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ የመጀመርያ ሙሉ አልበሙን ለማውጣት ተፍ ተፍ የሚለው ጃኪ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ጋር በህይወቱና በሙዚቃ ሙያው ዙሪያ እንዲህ አውግተዋል፡-

ሥራ ላይ ነው እንዴ ያደርከው? የደከመህ ትመስላለህ ?
አዎ ፤አልበም እየሰራሁ ነው፡፡ ሙሉ አልበም የማወጣው ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሆነ ጥሩ ስራ ለመስራት ቀን ከሌት እየተጋሁ ነው፡፡
ምን ዓይነት ዘፋኝ ነኝ ብለህ ነው የምታስበው? ባህላዊ ወይስ ዘመናዊ ?
አቅሜ ብዙ ነው ብዬ ነው የማስበው። ባህላዊውንም ዘመናዊንም እችላለሁ። ባህላዊ ሙዚቃን ሞደርን ለማድረግ ነው የምፈልገው፤የባህሉን ሙዚቃ ወጣቱ ትውልድ እንዲወደው እፈልጋለሁ፡፡ ባህሌን ስለምወድ ነው ወደ ባህላዊው የመጣሁት፡፡ ውጭ አገር ሬጌ ባንድ ውስጥ እንግሊዝኛ ሙዚቃ ነበር የምጫወተው፡፡ ያ ደግሞ እኔን አይገልፀኝም፤ እኔነቴን አይወክልም ብዬ ስለማምን ነው የተውኩት፡፡ በዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥም አለሁኝ፡፡ ባህላዊ ዘፋኝ ብቻ አይደለሁም። በአዲሱ አልበሜ ባህላዊ ዘፈን ብቻ አይደለም ይዤ የምቀርበው፤አቅሜንም ለማሳየት ስለምፈልግ ለአድናቂዎቼ የተለያዩ ነገሮች ነው የማቀርበው፡፡ ኢትዮጵዊ ቀለም ያላቸው ዘመናዊ ዘፈኖችን ነው የሰራሁት፡፡
ወደ ሙዚቃ ህይወት እንዴት ገባህ ?
በ13 ዓመቴ በህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት እሰራ ነበር፡፡ በቲያትር ቤቱ ውስጥ አማርኛ መዝፈን ጀመርኩ፤ መነሻዬ ያ ነው፡፡ ከዚያ ለሥራ ወደ ጀርመን አገር ሄድኩ፡፡ በሬጌ ባንድ ውስጥ የሬጌ ሙዚቃ እጫዎት ነበር፡፡ ኳየርም ነበርኩ። ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው ወደ አማርኛ ሙዚቃ የተመለስኩት፡፡ ራሴን ካገኘሁ በኋላ ማለት ነው፡፡ ሬጌ ሙዚቃ ዘፍኜ የሚሰጠኝ አስተያየት (ፊድባክ) አሁን እንደሚሰጠኝ አስተያየት አያኮራኝም ነበር። ዛሬ ‹‹ሰላ በይ›› ብዬ ዘፍኜ ከህዝብ የማገኘው ፍቅርና አድናቆት ኩራትና ደስታ ያጎናፅፈኛል፡፡ ራሴን እንደ ባህላዊ ዘፋኝ አድርጌ ብቻ አይደለም የምቆጥረው። በዘመናዊ ሙዚቃ በኩል ትውልዱ ባህሉን እንዲወድ የማድረግ አስተዋፅዖ ለማበርከትም እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ትውልዱ ዘመናዊነትን የሚከተል በመሆኑ ዘመናዊውን ቢሰማ ደስ ይለዋል፣ ሁለቱን በመቀላቀል ባህሉንም በዘዴና በጥበብ የበለጠ እንዲወደው ይሆናል፡፡ ወጣቱ ዘመናዊ ሆኗል፡፡ ቴክኖሎጂ ሲቀየር ሁሉም ሰው እያደገ ነው የሚመጣው፡፡ ወደ ኋላ ሄዶ የድሮውን ነገር ከሚያይ፣ የድሮው ዛሬ ላይ መጥቶለት ሲያይ የመቀበል ሁኔታው ይጨምራል፡፡
በህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት ውስጥ የማንን ሙዚቃ ነበር የምትጫወተው?
በድምፃዊነት ስሰራ ቲያትር ቤቱ ብቻ የሚያቀርበውን ነበር የምሰራው፡፡ በብዛት “እቴ ሜቴ”፣ “እንዲች እንዲች” የመሳሰሉ የልጆች ዘፈኖችን ነበር የምሰራው፡፡ የፍቅር ከሆነ ደግሞ ስለ እናት ነው፡፡ ለፍቅረኛ ወይም ስለ ፍቅር አልዘፍንም ነበር፡፡ ዕድሜያችን ያንን ለመዝፈን ስለማይፈቅድ፣ የሚመጡትም ወላጆች ከህፃናት ጋር ስለሆነ፣ እነሱን የሚያስተምር ሙዚቃ ነው የምንሰራው፡፡ በዛን ጊዜ በቲያትር ቤቱ ከጎናችን ሆነው ሲያግዙን የነበሩት እነ ሙሉ ገበየሁ፣ ዛሬ እዚህ ለመድረሴ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገውልኛል፡፡
ፕሮፌሽናል ድምፃዊ ነኝ ብለህ ታስባለህ ?
አዎ፡፡ በርግጥ ድምፃዊነት የእግዚአብሄር ተሰጥዖ ያስፈልገዋል፡፡ ያንን ጨምረሽ ት/ቤት ስትገቢ፣ ቴክኒካል ነገር ትማሪያለሽ፡፡ ለብዙ ነገር ይረዳል። ተሰጥዖ ብቻውን ምንም አይሰራም፤ተጨማሪ በትምህርት የሚመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ትንፋሽ አያያዝና ዜማ አያያዝ ላይ ትምህርቱ ይረዳል፡፡ ከሁሉም ግን ተፈጥሮ ይቀድማል፡፡
እንዴት ነው ወደ ጀርመን የሄድከው?
በ13 ዓመቴ ነው ለስራ የወጣሁት፡፡ መጀመርያ ከተለያዩ ታዋቂ አርቲስቶች ጋር ቲያትር ልናሳይ ወደ ፈረንሳይ ሄድን፡፡ ስራውን ከጨረስን በኋላ አክስት ስለነበረችኝ ወደ ኢትዮጵያ አልተመለስኩም፡፡ ሌሎች ሁለት ጓደኞቼም አልተመለሱም፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ኑሮዬ ውጪ ሆነ ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያ ነጠላ ዜማዬ እስኪወጣ ድረስ ውጪ ነበር የምኖረው፡፡
ውጭ ስንት ዓመት ኖርክ ማለት ነው?…
ወደ 13 ዓመት ገደማ ማለት ነው፡፡
ለምንድን ነው ጃኪ ጎሲ የተባልከው ?
ስሜ ጎሳዬ ቀለሙ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ለራሱ መለያ ስም ይሰጣል፡፡ የአርት ስሜ ነው ጃኪ ጎሲ፡፡
ጀርመንኛ ትችላለሃ ?
አዎ በደንብ እናገራለሁ፡፡
በጀርመንኛ መዝፈንስ ?
ጀርመንኛ አልዘፈንኩም፤ ቋንቋቸውን ብዙ አልወደውም፤ አያምርም፡፡ እናገረዋለሁ እንጂ እንኳን ለዘፈን ለምንም አይሆንም፡፡ ድምፅ ያለሽም አይመስል ብትዘፍኝበት፡፡
በቀለም ትምህርት ምን ያህል ገፋህ ?.
እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ነው የተማርኩት። ትምህርት ላይ ከልጅነቴ ጀምሮ ሰነፍ ነበርኩ። ሙዚቃ ብቻ ነበር የሚታየኝ፤ሌላ ምንም ነገር አይታየኝም፡፡ ውጪም ሳለሁ ሙሉ በሙሉ ፍላጎቴ ሙዚቃ ላይ ነበር፡፡ የሙዚቃ ስሜቴ ስለበለጠ፣ እንደምንም ገፍቼ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ብቻ ነው የተማርኩት፡፡
የምትታወቀው በአንድ ዘፈን ነው..በእሱም በዓለም ላይ እየዞረክ ነው…
ወደ አምስት ዘፈኖች አሉኝ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ያልመጡና ያልተለቀቁ፡፡ እዚህ ይታወቃል ብዬ የማስበው ሶስት ወይንም አራት ዘፈን ሊሆን ይችላል፡፡ ጭራሽ፣ የእኔ አካል፣ ደሞ አፌ፣ ሰላ በይ፣ ባንዲራው የታለ----እነዚህ ዘፈኖች በደንብ ነው የሚሰሙት---ተጨማሪ የመድረክ ስራዎችንም ይዤ እሄዳለሁ፡፡ የምወዳቸውን የታላላቅ አርቲስቶች ዘፈኖች ጨምሬ ነው የማቀርበው፡፡
በኮንሰርት የት የት አገራት ዞረሃል?
በቁጥር አላውቀውም፡፡ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ አረብ አገሮች፣ እስራኤል…በቅርብ ደግሞ ወደ አሜሪካ እሄዳለሁ፡፡ ከአሜሪካ በኋላ ሳውዝ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ሱዳን…አድናቂዎቼ እየጋበዙኝ ስለሆነ የምሄድባቸው ብዙ ቦታዎች አሉ- ከዛየን ባንድ ጋር፡፡ አሁን አብሬ እየሰራሁ ያለሁት ከዛየን ባንድ ጋር ነው፡፡ በጣም አሪፎች ናቸው፤ በጣም ደስተኛ ነኝ ከነሱ ጋር በመስራቴ፡፡ ከዛየን ባንድ ጋር የመጀመሪያ ኮንሰርቴን የሰራሁት በዱባይና አቡዳቢ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ከእኔ ጋር ናቸው፡፡ አሜሪካም አብረውኝ ይሰራሉ፡፡
ወደ አውሮፓ ስትመለስ በመደበኛነት ምንድነው የምትሰራው?ናይት ክለብ ውስጥ ትሰራለህ ?
ሬጌ ባንድ ውስጥ ነበር፤ አሁን ትቼዋለሁ፡፡ ‹‹ጭራሽ›› የሚለውን ዘፈኔን እስከሰራ ድረስ ከነሱ ጋር ነበርኩ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ብዙ ታዋቂ የሬጌ ዘፋኞች አሉ..ያ የእኔ ባህል አይደለም፤ የነሱ ባህል ነው፡፡ ብታወቅበትም ሪፕረዘንት አላደርግበትም፤እኔነቴን ስለማይገልፀው ይሆናል። ኢትዮጵያዊነቱን ይዤ የራሳችንን ባህል ትንሽ አሳድጌው ወጣቱ ትውልድም ሆነ ትላልቁ ሰው እንዲወደው ማድረግ ለእኔ አንድ ሃላፊነት ነው፡፡ ናይት ክለብ ላልልሽው አልሰራም፡፡
እዚህስ ኮንሰርት አላሰብክም ?
እዚህ ግብዣዎች አሉ፡፡ አልበሜ ሲወጣ ለማቅረብ መቆየትን መርጫለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኮንሰርት ማድረግ እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ እስከ አሁን የምጠብቀው አልበሜ ከወጣ በኋላ ከዛየን ባንዶች ጋር እዚህና አፍሪካ ውስጥ በደንብ ኮንሰርት እንሰራለን፡፡
“ሰላ በይልኝ” በሚለው ባህላዊ ዘፈንህ ላይ የምታሳየውን ባህላዊና ዘመናዊ የተደባለቀበት እንቅስቃሴ ኦሪጂናሉን እስክስታ እንደመበረዝ የሚቆጥሩ ወገኖች አሉ ---
በባህላዊ ዘፈን ላይ ዘመናዊ ዳንስ ነው የምደንሰው፡፡ ባህሉን ለማበላሸት ወይም ለመበረዝ አይደለም ዓላማዬ፡፡ ቢቱ ትክክለኛ ነው፤ አልቀየርነውም፡፡ ማሲንቆ አለው፡፡ ዜማ አወጣጤ የኢትዮጵያ ቀለም አለው፡፡ የቀየርነው ስታይሌንና አደናነሴን ነው፡፡ ያን ያደረግሁት ደግሞ ትውልዱን በዘመናዊ እንቅስቃሴ ለመሳብና ዘፈኑ ውስጣቸው ገብቶ እንዲወዱት፣እንዲኮሩበት ነው። ነጮች እንዲያዩትም ብዬ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ባህላዊ ሙዚቃ እየጠፋ ነው፡፡ ትላልቅ ክለቦች ብትሄጂ ..ባህላዊ ሙዚቃ መክፈት ሃጢያት ነው የሚመስላቸው፡፡ ከውጪ መጥቼ አንዳንድ ጊዜ ትላልቅ ክለብ ስሄድ፣ የውጪ ዘፈን ብቻ ነው የሚደመጠው፡፡ አገሬ ላይ ሳይሆን እዛው ያለሁ ነው የሚመስለኝ፡፡ እና ውስጤ ዘመናዊነትም ባህላዊነትም አለ፡፡ ያንን አቀናጅቼ ውጤት ለማምጣት ነው የሞከርኩት፡፡ ያንንም አምጥቼዋለሁ፡፡
እስክስታ ላይስ እንዴት ነህ ?
/ሳቅ/ እስክስታ የለመድኩት ከ“ሶራዎች” ነው፡፡ ለ“ሰላ በይ” የሙዚቃ ክሊፕ ለመስራት ገጠር ሄደን ነው የ“ሶራ”ን ባንድ ያየሁት፡፡ በጣም ተደነቅሁኝ። “ሶራ”ን ይዘው ሲመጡ ለእኔ አዲስ ነገር ነበር --- ከተለመደው ውጪ ስለሆነ፡፡ ደስ የሚል የእስክስታ አብዮት (ሪቮሉሽን) ነው የፈጠሩት፡፡ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ የትም ብትሄጂ ደግሞ የእነሱ ተፅዕኖ አለበት። በሁሉም ቦታ እንደዚህ ዓይነት ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ .“ሶራ” ባይቀጥልም ሌላ ሪቮሉሽን ያስፈልጋል፡፡
“ሰላ በይ” ምን ማለት ነው?
ፈታ በይ፣ አንቺ ፈታ ካልሽ ፍቅርም ይፍታታል። ሰላ ካልሽ በመካከላችን ፍቅርና ሰላም ይወርዳል---ነገር አለማክረር ማለት ነው፡፡
በቅርቡ ደግሞ ለብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድናችን “ትውልዱ ፍም እሳት ነው”የሚል አዲስ የሙዚቃ ክሊፕ ከናቲ ማን ጋር ሰርታችኋል፡፡ እውነት ትውልዱ ፍም እሳት ነው?እንዴትስ ይገለፃል?
ናቲ ለሶስት ቀን አውሮፓ መጥቶ በሶስት ቀን ውስጥ ነው የሰራነው፡፡ ቃልዋን በአጋጣሚ እሱ ነው ያመጣት - ‹‹ፍም እሳት›› የምትለውን፡፡ ለዚህ ትውልድ ምን እንስራ ብለን እየተነጋገርን ነበር…‹‹ይሄ ትውልድ ፍም እሳት ነው›› የሚለውን ነገር ሲያመጣ እኔም አመንኩበት፡፡ ሙዚቃውን ያቀናበረው ዮኒ ውብ ይባላል፡፡ እዛው ጀርመን ነው፡፡ ጓደኛዬ ነው። የእኔን ክፍል እኔ ፃፍኩት፡፡ ናቲም የራሱን ክፍል ፃፈ- ‹‹ፍም እሳት›› የሚለውን፡፡
በፍቅር ያመነ፣ በቃል የፀና፣
ሀረጉን የማይመዝ ይከተለን እና
በእኛው ቅኝት ገብቶ ይህን ሰምቶ
የእውነትን ዘር ዘርቶ
ተማምኖ የሚኖር ተከባብሮ
ጥላቻን አርቆ ሽሮ
‹‹ሃይለኛ ትውልድ›› ማለት ነው፤በአሉታዊ መልኩ ሳይሆን በአዎንታዊ --- ‹‹ማሰብ የሚችል፣ ፈጣን›› እንደማለትም ነው፡፡ አንቺን ለመውደድ ‹‹አማራ ነሽ፣ ትግሬ ነሽ፣ ኦሮሞ ነሽ፣ ከየት ነሽ፣ ወዴት ነሽ፣ የት ነው ያደግሽው?›› ማለት አይገባኝም፡፡ ለእኔ አበባየሁ መሆንሽ ብቻ ይበቃኛል፡፡ ይሄ በአገር ውስጥም በውጪም ያለውን ይመለከታል፡፡
እስካሁን ከአገርህ አርቲስቶች ጋር ኮንሰርቶች አቅርበሃል?
ከአስራ አምስት ቀን በፊት ከሄለን በርሄ ጋር ዱባይና አቡዳቢ ላይ ሰርቻለሁ፡፡ ከጂጂ ጋር ጀርመንና ሆላንድ፡፡ ብዙ ታዋቂ ሳልሆን ደግሞ ከአስቴር አወቀ ጋር ሰርቻለሁ፡፡ ሁሉም አበረታተውኛል፡፡ አስቴር አወቀ ‹‹ልጅ ነህ በርታ፤ጥሩ ነው ያለኸው›› ብላኛለች። ጂጂ እንደውም ከማደንቃት ነገር--- ያኔ እኔ ሃሳቤ ሁሉ በሬጌ ውስጥ ስለነበር---አንድ አማርኛ ሬጌ ዘፍኜላት “በጣም አሪፍ ነው” ብላ እንደውም ማሲንቆ ክተትበት አለችኝ፡፡ ሬጌ ዘፈኑ ላይ እኮ ነው። በጣም አልረሳትም፡፡ ማሲንቆ እዚህ አገር ርካሽ ተደርጎ ነው የሚቆጥረው፤ሰው ዋጋውን በደንብ አላወቀውም። ውጪ አገር ግን አነጋጋሪ ነው፡፡ ማሲንቆ ስሰማ ሊወረኝ ይችላል፡፡ ባህል ሙዚቃ ውስጥ ማሲንቆ ነው ትልቅ ሚና የሚጫወተው፡፡
ማሲንቆ መጫወት ትችላለህ?
አልችልም፤ ብችል ደስ ይለኛል፡፡ ኪቦርድ እሞክራለሁ፣ ቦክስ ጊተር እየተማርኩ ነው፡፡
በግራና ቀኝ እጅህ ላይ እንዲሁም አንገትህ ላይ የተነቀስከው ነገር ትርጉም አለው ?
አዎ፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ነው ጀርመን የተነቀስኩት፡፡ እጄ ላይ በህይወት የሌሉትን የእናትና አባቴን ስም ነው የተነቀስኩት፡፡ አንገቴ ላይ ደግሞ የሙዚቃ ኖታ ነው፡፡ ሙዚቃ ህይወቴ የሚለውን ለመጠቆም፡፡ በዚች ምድር ላይ የምወዳቸውን ሶስት ነገሮች ነው የተነቀስኩት፡፡
ሙዚቃህ በዩቲዩብ ተወዳጅ ሆኗል፡፡ ለመሆኑ ስንት ሰው ጎበኘው?
አንዱዋን ብቻ ነው የምነግርሽ፡፡ ‹‹ጭራሽ›› የሚለው ለምሳሌ 3 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ‹‹ሰላ በይ›› የሚለው ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ይሆናል፡፡ የተለያየ አካውንት ላይ የተለቀቁትን ብታይ ግን አምስት ሚሊዮን ይደርሳል፡፡
የሙዚቃህ አድናቂዎች እነማን ናቸው?
ወጣቱ ትውልድ ነው በደንብ የተቀበለኝ። ትላልቆቹ መጀመሪያ ላይ አልተቀበሉትም ነበር፤እየቆዩ ሲሄዱ ግን እየገባቸውና እየወደዱት መጡ፡፡ አሁን መንገድ ላይ ሲያገኙኝ ያበረታቱኛል።
ፍቅረኛ አለህ?
የለኝም፡፡ ለጊዜው ፍቅረኛዬ ሙዚቃ ናት፡፡

Published in ጥበብ

አሜሪካ ያልሰለለችው “እግዚአብሔርን” ብቻ ነው!
የመብራት መጥፋት ዋናው ችግር የ”ጠባቂነት” ባህል ነው!
የኤሌክትሪክ ኃይል በየግቢያችን ልናመነጭ ነው!

እውነቱን ልንገራችሁ አይደል----ያሳለፍነው ሳምንት የአግራሞት ነው፡፡ የአሜሪካንን የስልክ ጠለፋና የስለላ ጦስ ሰማችሁልኝ አይደል? እንዴ --- አንድዬን ብቻ እኮ ነው ያልሰለለችው! (የሚጠለፍ ስልክ የለማ!) እኔማ ምን እንደመሰለኝ ታውቃላችሁ? በቃ -- በልጅነቴ እሰማው የነበረው 8ኛው ሺ የገባ ነው የመሰለኝ፡፡ እስቲ አስቡት---የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርከል፤ለአስር ዓመት ስልካቸው እየተጠለፈ ተሰልለዋል፡፡ እሺ--- መሪዎቹስ እርስ በእርስ ይተዋወቁ ይሆናል፡፡ 30 ሚሊዮን የፈረንሳይ ዜጎች፣ 60 ሚሊዮን የስፔይን ዜጎች ስልካቸው ተጠልፎ መክረሙ ምን ይባላል? ግን አሜሪካ ከስልክ ጠለፋ ውጭ ሥራ የላትም ማለት ነው ? አንድ ነገር ግን ፈርቻለሁ፡፡ ይሄ የፀረ-ሽብርተኝነት ዘመቻ ዓለምን አካክዶ መተማመን ታሪክ ሆኖ እንዳይቀር! አሁን አንጌላ መርከል ዳግም ለአሜሪካ ልባቸውን የሚሰጡ ይመስላችኋል? (10 ዓመት እኮ ነው የተሰለሉት!) ወይ አሜሪካ---ሽብርተኝነትን እዋጋለሁ ብላ ዓለሙን ሁሉ በሽብር ሞላችው! (እሾህን በእሾህ አሉ !)
ከሁሉም የገረመኝ ደግሞ ኦባማ ስለስልክ ጠለፋው ምንም የማውቀው የለም አሉ መባሉ ነው፡፡ እኔ የምለው ግን ----- ምነው ቻይና ድምጿ ጠፋ? (መንገድ ብቻ ነው የምጠልፈው ለማለት ነው?) “ኃያል መንግስትን ማመን ቀብሮ ነው” አለች- ጀርመን! እንዴ--- እዚህም አገር እኮ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን ስልክ ይጠልፋል ተብሎ እንደጉድ ተወርቶ ነበር፡፡ እሱ እንኳን ያምርበታል። የጀመረውን ልማት ሳይጨርስ በጎዳና ላይ ነውጥ ከሥልጣን ሊያወርዱኝ ይፈልጋሉ ብሎ የጠረጠራቸውን ይሆናል የጠለፈው፡፡ (ይሆናል እኮ ነው!) ቢያንስ ቢያንስ ኢህአዴግ እንደ አሜሪካ--- የ60 ሚሊዮን ህዝብ ስልክ ይጠልፋል ብዬ አላስብም (ቴክኖሎጂውም እኮ መከራ ነው!) “የአሜሪካ ሬዲዮ ድምፅንም “ጃም” ያስደረገው በቻይና ድጋፍ ነው” የሚሉት ምቀኞች ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ለነገሩ ህዝባዊ መሰረት ያለው ፓርቲ እኮ ህዝቡን አይሰልልም! (በጆሮ ጠቢና በካድሬ አልወጣኝም!) ሞባይልና ኢሜይላችንን በመጥለፍ ማለቴ ነው! ቢሰልልስ ከእኛ ምን ያገኛል? ኢህአዴግ የማያውቀው ኑሮ ከየት እናመጣለን፡፡ እሱ ሰፍሮ የሰጠንን እኮ ነው የምንኖረው፡፡ (የህዝቡን ገበና የሚያውቅ ፓርቲ አይሰልልም!)
አሁን ከስለላ ወደ ኢቴቪ ልውሰዳችሁ፡፡ እውነቱን ልንገራችሁ አይደል --- ምን ቢያበግነኝ ኢቴቪን ጠልቼ አልጠላውም፡፡ (ምርጫ የለኝማ!) ማታ ማታ ኤልፓ ካልጠመመብኝ በቀር --- ብቸኝነቴን የሚያረሳሳኝ ኢቴቪ እኮ ነው፡፡ እኔ የምለው… ኢቴቪ ከዜናና ከፕሮፓጋንዳ በስተቀር ሌሎቹን ፕሮግራሞች በሙሉ ለ”ልማታዊ” ባለሃብቱ ሊቸበችበው ነው የሚባለው እውነት ነው እንዴ? (ኢህአዴግ “ልብ ገዛ” በሉኛ!) ትንሽ ፍራቻ ግን አለኝ! “የቴሌቪዥን ጣቢያውን ኒዮሊበራሊስቶች በእጅ አዙር ቢቆጣጠሩትስ?” የሚል፡፡ (መሠረተ ቢስ ፍራቻ ከሆነ እታረማለሁ!)
ባለፈው ማክሰኞ ማታ በኢቴቪ ያየሁትን አስገራሚ ነገር ልንገራችሁ፡፡ (ሳምንቱ የአግራሞት ነው ብዬ የለ!) ኢቴቪ ፊት ለፊት ጉብ ብዬ የለመድኩትን በፕሮፓጋንዳ ቅቤ የታሸ ዜና እኮመኩማለሁ፡፡ (“እንደምን አመሻችሁ ዲሽ የሌላችሁ?” አልቀረም እንዴ?) ልክ ዜናው ሲጠናቀቅ የአየር ትንበያ መጣ፡፡ የነገውን የአየር ትንበያ ለመስማት አሰፍስፌ ሳለ የትንበያ ማረምያ ሰማሁ -“ትላንት ያቀረብነው የአየር ትንበያ ስህተት ስለሆነ ይቅርታ እንጠይቃለን!” የሚል፡፡ ይሄ ለትያትር ግብአት እንጂ ለReal life አይመችም፡፡ ነገርዬውን የበለጠ ኮሚክ ያደረገው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ከይቅርታው በኋላ “አሁን ወደ እለቱ የአየር ትንበያ እናልፋለን” መባሉ ነው፡፡ ለነገሩ አብዛኞቻችን ከቤት የምንወጣው ሰማዩን አንጋጠን አይተን እንጂ የአየር ትንበያን ሰምተን አይደለም፡፡
አንዱ የሸገር ሰው ነው አሉ፡፡ የነገውን የአየር ሁኔታ ለማወቅ ይፈልግና ወደ አየር ትንበያ ቢሮ ስልክ ይመታል “ጌታዬ… የነገውን የአየር ትንበያ ለማወቅ ፈልጌ ነበር… ሊነግሩኝ ይችላሉ?”
ስልኩን ያነሳው የአየር ትንበያ ባለሙያም፤ “የነገውን ነው የፈለከው አይደል?” መልሶ ጠየቀው።
“በትክክል ጌታዬ!” ይላል ፤ትሁቱ የአየር ትንበያ ጠያቂ፡፡
“ወይ ይዘንባል ወይ አይዘንብም!” ብሎት እርፍ አለ፤ የአየር ትንበያ ቢሮው ሠራተኛ፡፡ (ሳይንስ ቀለጠች አትሉም!)
እኔ የምላችሁ… ባለፈው ቅዳሜ የመቀሌው “አሽጎዳ የነፋስ ኃይል” ሲመረቅ ተመልክታችኋል? (በኢቴቪ Live ነበር እኮ!) እኔን ግን ከነፋስ ኃይሉም የበለጠ ያስደመመኝ ምን መሰላችሁ? የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ምህረት ደበበ የተናገሩት፡፡ “የዓመቱ ተጠቃሽ ንግግር” ልትሉት ትችላላችሁ፡፡
“ይሄን ያህል ምን ቢናገሩ ነው?” ብላችሁ ይሆናል፡፡ (የመብራት መቆራረጥና መጥፋት ችግር ቁርጥ ምላሽ ያገኘበት ታሪካዊ ንግግር ነበር!) እናላችሁ… ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ተደጋጋሚ እሮሮና አቤቱታ የበዛበትን የመብራት መቆራረጥና መጥፋት በተመለከተ እንዲህ አሉ -“ችግሩ የኃይል አቅርቦት አይደለም፤ የ“ጠባቂነት” ባህል ነው” (“እቺ ናት አገርህ” የምትለዋ ግጥም ትዝ አለችኝ) ለካስ እስከዛሬ “የመልካም አስተዳደር ችግር ነው”፣ “የሴረኞች ደባ (Sabotage) ነው” ወዘተ… የተባለው ሁሉ ቀብድ ነው - ሃቋን እስክንሰማ! ይኼው ሥራ አስፈፃሚው እግዜር ይስጣቸውና በእለተ ቅዳሜ ከመቀሌ ምድር ”የመንግስት መብራት ጠባቂ” መሆን እንደሌለብን በማይጎረብጥ አንደበታቸው እቅጯን ነገሩን፡፡ (ደፋር አይጥፋ!)
አንዳንዴ የኢህአዴግ ሹማምንት “ወጣቶች የመንግሥት ሥራ ጠባቂ መሆን የለባቸውም!” ሲሉ ሰምታችሁ አታውቁም? ሥራ አስፈፃሚውም እንደዚያ ነው ያሉን፡፡ “የመንግስት መብራት አትጠብቁ!” እቅጩን መናገራቸው ቢያስደስተኝም ትንሽ ቅር ያለኝ ነገር አለ፡፡ “ከመብራት ጠባቂነት” እንዴት እንደምንላቀቅ ትንሽ ፍንጭ እንኳን አልሰጡንም፡፡ በጀነሬተር ይሁን በነፋስ ኃይል አሊያም በፀሃይ ብርሃን ወይም በእንፋሎት ወይም በባዮጋዝ-- አልነገሩንም፡፡ (“ፍንጭ ጠባቂ” ሆንኩባችሁ?)
የሆኖ ሆኖ ግን ጠባቂ መሆን የለባችሁም ተብለናል፡፡ እናም---በየአካባቢያችን በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተን ---- ወንዞችና ኩሬዎችን እየፈለግን ሃይል ማመንጨት አለብን! ወንዝና ኩሬ የሌለበት ሰፈር ሲሆን ደግሞ የነፋስ ኃይል ማመንጨት ነው (የግድ እኮ የአባይ ዓይነት ግድብ አያስፈልገንም!)
አንድ ቀን ደግሞ የኢትዮ-ቴሌኮም ኃላፊ ተነስተው “ህብረተሰቡ የመንግሥት ኔትዎርክ ጠባቂ መሆን የለበትም” ማለታቸው አይቀርም፡፡ እናም --- እንደምንም ከ“ኔትዎርክ ጠባቂነት” መላቀቅ አለብን ባይ ነኝ! (አሁንማ እስኪነገረን አንጠብቅም!)
ከጥቂት ሳምንት በፊት የዳቦ ዘር ጠፍቶ አዳሜ መንግስት መንግስትን ሲያይ ነበር፡፡ ሰሞኑን ስንዴ በሽበሽ መሆኑን ጠ/ሚኒስትሩ በኢቴቪ ሲናገሩ ሰማሁ፡፡ የትጉህ ገበሬዎችን ማሳ የጎበኙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በድል አድራጊነት ስሜት ተጥለቅልቀው “ስንዴ የምንሸጥበት የውጭ ገበያ እናፈላልጋለን” ብለዋል፡፡ (“በቆሎም ኤክስፖርት እናደርጋለን ተብሎ ነበር” እንዳትሉኝ!) በነገራችን ላይ ስንዴ ለውጭ ገበያ እናቀርባለን ማለት እኮ አገሩ በዳቦ ይጠግባል ማለት አይደለም፡፡ እናላችሁ---የስንዴ እጥረት ተፈጥሮ “የመንግስት ስንዴ ጠባቂ አትሁኑ!” የሚል ተግሳፅ ሳይደርሰን በፊት በየጓሮአችን የአቅማችንን ያህል ስንዴ የመዝራት ባህል ማዳበር አለብን ባይ ነኝ፡፡
አያችሁ… ለአንዳንድ ነገሮች ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ በአንድ ወቅት እንደተከሰተው አይነት የዘይት እጥረት ቢፈጠር ምን ይውጠናል? መንግስት እንደሆነ እንኳንስ ዘይት መብራትም ቢሆን እራሳችሁ አምርቱ እንጂ እኔን ጠባቂ መሆን የለባችሁም ብሎ ተፈጥሟል፡፡ እናም… መፍትሄው ምን መሰላችሁ? አሁኑኑ በየቤታችን ዘይት መጭመቅና ማምረት መጀመር አለብን፡፡ የ“መንግስት ዘይት ጠባቂ” መሆን እኮ አይፈቀድም፡፡ በነገራችሁ ላይ --- ሰሞኑን ሸንኮራ አገዳ ጓሮዬ ለመትከል አስቤአለሁ። የራሴን ስኳር የማምረት እቅድ አለኝ፡፡ “የመንግስት ስኳር ጠባቂ” ላለመሆን!
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል --- የመብራት ኃይል ኮርፖሬሽኑ ሃላፊ ባለፈው ቅዳሜ የነገሩንን ነገር ትንሽ ቀደም ቢያደርጉልን ኖሮ፣ እስካሁን የምንም ነገር “ጠባቂ” አንሆንም ነበር፡፡ ነጋ ጠባ በትራንስፖርት ችግር ከመማረር ይልቅ የራሳችንን የትራንስፖርት አማራጭም እንፈጥር ነበር። ግዴለም አሁንም ቢሆን… የታክሲው እጥረት አልተፈታምና በየእድራችን፣ ማህበራችን ወዘተ እንምከርበት፡፡ አንድ ቀን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ “ችግሩ የህዝቡ ታክሲ ጠባቂ መሆን ነው!” ማለቱ አይቀርማ፡፡ ይሄውላችሁ---ከበረታን ምንም የማንፈታው ችግር የለም፡፡ ትንሽ የሚያስቸግረን ምን መሰላችሁ? የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ (ዶላር እንደ ስንዴ ጓሮ አይመረትም!) በነገራችሁ ላይ --- በየአካባቢያችን የየራሳችንን የአየር ትንበያ መጀመር እንዳለብንም አንድ ወዳጄ ሹክ ብሎኛል። ለምን መሰላችሁ? “የመንግስት የአየር ትንበያ ጠባቂ” ላለመሆን ነው፡፡ እንደሰሞኑ የትንበያ ስህተት ሲፈጠርም ጣታችንን መንግስት ላይ ከመቀሰር ይገላግለናል፡፡
እግረ መንገዴን ---- ተቃዋሚዎችም እንደኛ በሁለት እግራቸው መቆም ይለምዱ ዘንድ እመክራቸዋለሁ (ነፃ ምክር እኮ ነው!) አያችሁ---የፖለቲካው ምህዳር ጠቧል፣ዲሞክራሲው ቀጭጯል፣ህገመንግስታዊ መብቶች እየተደፈጠጡ ነው፣ኢህአዴግ ሥልጣን የሙጥኝ ብሏል ወዘተ---የሚሉ ብሶቶች የሚተረጎሙት እንደጠባቂነት ነው፡፡ እናም አንድ ቀን ኢህአዴግ “የተቃዋሚዎች ችግር የጠባቂነት ነው” ማለቱ አይቀርም፡፡ እስቲ አሁን እንኳ ወግ ደርሷቸው ይቅደሙት! በነገራችሁ ላይ ---- ዜጎች (እኛ) ከመንግስት ጠባቂነታችን ሙሉ በሙሉ ስንላቀቅ ከመንግስት ጋር ያለንም ውል ይፈርሳል፡፡ መንግስት ላያስፈልገን ሁሉ ይችላል፡፡ (መብራት ከራሳችን፣ ስንዴ ከጓሮአችን፣ ኔትዎርክ በብልሃታችን፣ሰላምና ፀጥታ በማህበረሰብ ፖሊሳችን---)

በአሜሪካ ስለላ ድፍን አውሮፓ ተናውጧል!
የመከላከያና የደህንነትን ነገረ ስራ ጉዳዬ ብለው የሚከታተሉ ባለሙያዎች፤ ሰላይና ተሰላይ በአንድ ጣራ ስር አድፍጠው የየፊናቸውን ጉዳይ የሚከውኑበት መስሪያ ቤቶች ቢኖሩ የስለላ ድርጅቶች ብቻ ናቸው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለው ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ሁሌም የሚጠቀሙበት አንድ አሪፍ አባባል አላቸው፡- “በሬ ካራጁ ይውላል” ይላሉ፡፡ 
የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ይህ አባባል በረጅም የአገልግሎት ዘመኑ ለበርካታ ጊዜ ተጠቅሶበታል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ሌሎችን ለመሰለል የቀጠራቸው ሰላዮቹ፣ ራሱን መልሰው በመሰለል የመከዳትን መራራ ጽዋ ወዶ እስኪጠላ ድረስ ሲግቱት ኖረዋል፡፡
ኤንኤስኤ በሚለው አጭር ስያሜው ይበልጥ የሚታወቀው ብሔራዊ የደህንነት ድርጅት አሜሪካ ካሏት የተለያዩ የመረጃና የደህንነት ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ የዚህ ድርጅት የምሰረታ ታሪክ ልብወለድ ይመስላል፡፡
በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካ የመገናኛና የኤሌክትሮኒክ ባለሙያዎች፤ የጀርመንንና የጃፓን ከፍተኛ ወታደራዊ ሚስጥሮችን ኮድ በመስበር በአሜሪካ ይመራ ለነበረው የተባበረው የጦር ሃይል መሪዎች ያስተላልፉ ነበር፡፡ በተለይ የጀርመንን የ“U - Boat” ከፍተኛ ወታደራዊ ሚስጥር ኮድ በመስበር ያቀበሉት መረጃ፣ የተባበረው የጦር ሀይል በሰሜን አትላንቲክና በፓስፊክ አውደግንባሮች ከፍተኛና ወሳኝ ድሎችን እንዲቀዳጅ አስችሎታል፡፡
ይህንን ሁኔታ በትኩረት ይከታተሉ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሀሪ ትሩማን፤ የባለሙያዎችን የሚስጥር ኮዶችን እየሰበሩ የጠላትን ጓዳ ጐድጓዳ የመበርበር ተግባር፣ ከጦርነቱ በኋላም በሚገባ ለመጠቀም ስለሚቻልበት ሁኔታ ተጨማሪ ጥናት እንዲደረግ አዘዙ፡፡ በትዕዛዛቸው መሠረትም ጥናቱ ተካሂዶ ውጤቱ ቀረበላቸው፡፡
ፕሬዚዳንት ትሩማን የቀረበላቸውን የጥናት ውጤት ከአማካሪዎቻቸው ጋር ከገመገሙ በኋላ፣ ብሔራዊ የደህንነት ድርጅት በሚል ስያሜ በዋናነት “የጠላትን” የግንኙነት መረቦች በመጥለፍ፣ የምስጥር ኮዶችን በመስበር፣ በተለይም በጠላትነት የተፈረጁ ሀገራትን መሪዎች፣ ከፍተኛ የሲቪልና የጦር ሃይል አዛዦችን ማናቸውም አይነት የኤሌክትሮኒክ ግንኙነቶች በመጥለፍ መረጃ እንዲሰበስብ ስልጣንና ሃላፊነት በመስጠት ህዳር 4 ቀን 1952 ዓ.ም እንዲቋቋም አደረጉ፡፡
ድርጅቱ የተቋቋመው ከጦር ሃይሉ፣ ከስለላ ተቋማት፣ ከቴክኖሎጂ የምርምር ተቋማትና ከሌሎች ምሁራን የተውጣጡ ምርጥና ብቁ ባለሙያዎችን በመያዝ ነበር፡፡ ይህ ጠንካራ የሰው ሀይሉ በተለይ በበርካታ አሜሪካውያን ዘንድ እንኳን ሰው ይቅርና ነፋስም በውስጡ አስርጐ የማያስገባ፣ ሁለመናው ድፍንና ለምንም አይነት አደጋ ያልተጋለጠ፣ እጅግ ጠንካራ የስለላ ድርጅት ተደርጐ እንዲቆጠር ምክንያት ሆኖት ቆይቷል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህ የድርጅቱ ስዕል የውሸት ነበር፡፡ እንደ ሲአይኤ ሁሉ ይሄውም ድርጅት ከአራጁ ጋር የሚውል በሬ ነበር፡፡
ወጣቱና መልከ መልካሙ ኤድዋርድ ስኖውደን በኮምፒውተር እውቀቱ፣ በመረጃ አያያዝና ትንተና ችሎታው እኔ ነኝ ያለ ድንቅ ባለሙያ ነው፡፡ ለስራውና ለሚሰራበት ድርጅት የነበረው ጥብቅ ታማኝነትም በተለያዩ መስሪያ ቤቶች አብረውት በሰሩ አለቆቹና ባልደረቦቹ ተመስክሮለታል፡፡
ብሔራዊ የደህንነት ድርጅት እምነት ጥሎበት ቁልፍ በሆነ የመረጃ ምስጢራዊ የስራ ቦታ ላይ በከፍተኛ ደመወዝ የቀጠረውም በዚህ የተነሳ ነበር፡፡ በኤድዋርድ ስኖውደን አዕምሮ ውስጥ ግን የተመሠከረለት ታማኝነት ሳይሆን በሬውን የማረድ ሃሳብ ይመላለስ ነበር፡፡ ስኖውደን በሬውን ለማረድ የሚጠቀምበት ካራ፣ በእውቀትና፣ በችሎታ የተካኑት ጣቶቹ ነበሩ፡፡
እናም ከጥቂት ወራት በፊት እጅግ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ከፍተኛ የአሜሪካ ምስጢራዊ መረጃዎች በረቀቀ ስልት ለህዝብ ይፋ በማውጣት፣ የበሬውን አንገት ክፉኛ ካረደ በኋላ ተሰዶ ሞስኮ ገባ።
ከዚያ በኋላ ያለው ጊዜ ለብሔራዊ የደህንነት ድርጅቱ እስከወዲያኛው ድረስ አይመልሰው የሚያሰኝ ነው፡፡ ኤድዋርድ ስኖውደን ለህዝብ ይፋ እንዲሆኑ በበተናቸው እጅግ በርካታ ሚስጥራዊ መረጃዎች የተነሳ አሜሪካ ፈፅሞ አይታው በማታውቀው የዲፕሎማሲ ቅሌት ውስጥ እስከ አፍንጫዋ ተዘፈቀች፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የብሔራዊ ደህንነት ድርጅት፤ የመሪዎቿን፣ ከፍተኛ የሲቪልና ወታደራዊ መሪዎቿን የኤሌክትሮኒክስ ግንኙነቶች በመጥለፍ ለረጅም ጊዜ ስትሰልላት እንደነበር ያወቀችው ብራዚል፤ አሜሪካንን በማውገዝና ለአለም በማጋለጥ አገር ይያዝልኝ አለች። ከብራዚል ቀጥላ የቤቷን ጉድ ያወቀችው ሜክሲኮም “የመልካም ጉርብትናና የክፉ ቀን አጋርነት ውለታዬ ይሄ ሆነ ወይ” በማለት አሜሪካ ላይ የእርግማን መአት በማውረድ፣ እሪ እምቧ አለችባት፡፡ ሌሎች የደቡብ አሜሪካ ሀገራትም ለብራዚልና ሜክሲኮ ያላቸውን ወዳጅነት ለመግለጽ አሜሪካን “ደረቅ አይናውጣ!”፣ “ይሉኝታ ቢስ ወራዳ!” በማለት ተጨማሪ ውግዘት አወረዱባት፡፡
ይህን ጊዜ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ የብሔራዊ የደህንነት ድርጅቱን መሪዎች አስጠሩና “እንዴት ነው ጐበዝ! ይህ ሁሉ የውግዘትና የእርግማን መአት የወረደብን? ለመሆኑ ምኑን ከምን ብታደርጉት ነው? እንዲያው ስራችሁ ግን ምንድን ነው?” በማለት የአለቅነታቸውን ጥያቄ አቀረቡ፡፡ የብሔራዊ ደህንነት ድርጅት መሪዎችም፤ በአዋጅ በተሰጠን ስልጣንና ሃላፊነት መሠረት እንዲህ ያሉና እንዲህ የመሰሉ ስራዎችን እንሰራለን፡፡
ከእነዚህ ስራዎቻችን አንዱና ምናልባትም ዋነኛው “Head of state collection” ይባላል በማለት መልስ ሰጡ፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ ከቀረበላቸው መልስ “Head of state collection ከሚለው በስተቀር ሌላው ግልጽ ሆኖላቸው ነበር፡፡
ይሄኛውን ግን “ለመሆኑ ምን ማለት ነው” እያሉ ለራሳቸው ሲያሰላስሉ ከቆዩ በኋላ፣ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ሳይጠይቁ እነሱም ሳይሰጧቸው በዚሁ ተለያዩ፡፡
የዚያኑ ቀን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከባለቤታቸውና ከሁለት ሴት ልጆቻቸው ጋር የባለቤታቸው እናት ያዘጋጁላቸውን ሰላጣና አሳ ተመግበው ሲያበቁ፣ ከመተኛታቸው በፊት አምላክ እርግማኑንና ውግዘቱን በብራዚልና በሜክሲኮ በቃህ እንዲላቸው ፀሎታቸውን አቅርበው ነበር፡፡
ከሶስት ቀን በኋላ የተከሰተው ነገር፣ የፕሬዚዳንት ኦባማ ፀሎት እንዳልተሠማ ይልቁንም ኢትዮጵያውያን “የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል” የሚሉት አባባል እንደደረሰባቸው አረጋገጠ፡፡
መዘዘኛው ኤድዋርድ ስኖውደን፤ ለህዝብ ይፋ ያደረገው ምስጢራዊ መረጃ አሜሪካ ፈረንሳይን ለአመታት ስትሰልላት እንደነበር አጋለጠ፡፡ ፈረንሳውያን በተቃውሞ “አገር ይያዝልን!” አሉ። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንድም እሳት ለብሰው፣ እሳት ጐርሰው ለፕሬዚዳንት ኦባማ ስልክ በመደወል ተቃውሟቸውንና ስሞታቸውን ካቀረቡ በኋላ፣ ስለጉዳዩ ይፋ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ ይሁን እንጂ ከአሜሪካ ዘንድ ያገኙት መልስ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ የኤሊዜ ቤተመንግስት መግለጫ አመለከተ፡፡
ፈረንሳይ ያስነሳችው አቧራ ጭሱ ገና እንኳ ገለል ሳይል፣ አሜሪካ ስልሳ ሚሊዮን የሚሆኑትን ስፔናውያን የስልክ ንግግራቸውንና የመልዕክት ልውውጣቸውን እየጠለፈች ስትሰልላቸው እንደነበር ኤልሙንዶ የተሰኘው ጋዜጣ አጋለጠ። አሜሪካና ፕሬዚዳንቷ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በቅሌት ላይ ቅሌት ተደራረበባቸው፡፡
የሆኖ ሆኖ ነገሩ ወይም የቅሌቱ ማዕበል በዚህ ቢያበቃ ኖሮ፣ አሜሪካና ፕሬዚዳንት ኦባማ እፎይ ባሉና በተገላገሉ ነበር፡፡ የስፔናውያን የተቃውሞ ጩኸት ገና ተግ ሳይል የጀርመኑ ጉድ ፈነዳ፡፡ አሜሪካ Head of state በተሰኘው የብሔራዊ የደህንነት ድርጅት የስለላ መርሀ ግብር አማካኝነት ጀርመንን በተለይም ደግሞ የቻንስለር አንጌላ መርከልን ተንቀሳቃሽ ስልክ በመጥለፍ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ስትሰልል እንደቆየች መረጃው በይፋ ተጋለጠ፡፡
ይህን ጊዜ ድፍን አውሮፓ ከዳር ዳር ተናወጠ፡፡ የአውሮፓ ህብረት ይህን የአሜሪካ ነውረኛ ድርጊት ከዋነኛ አጀንዳዎቹ አንዱ አድርጐ የሚነጋገር ዘጠኝ አባላት ያሉት የልዑካን ቡድኑ መሪ የሆኑትን ቪቪያን ሪዲንግ፤ “ጓደኛሞችና አጋሮች እርስበርሳቸው አይሳለሉም፤ ይህ ቀላል መርህ ነው፡፡ አሁን የተፈጠረው የመተማመን ቀውስ ነው፡፡ የእርስ በርስ መተማመን ሳይኖር የጋራ አጀንዳ የሆነውን የንግድ ስምምነት እንዴት መገንባት እንችላለን” በማለት የሁኔታውን ከባድነትና አስቸጋሪነት ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርከል፤ የአሜሪካ አጋር፣ በተለይ ደግሞ የፕሬዚዳንት ኦባማ የቅርብ ወዳጅ በመሆናቸው “አሜሪካ ትሰልለኛለች” ብለው እንዳያስቡ አድርጓቸው ነበር፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ በ2009 ዓ.ም እሳቸውና 5250 የሚሆኑ የጀርመን ሚኒስትሮችና ሌሎች ባለስልጣናት ተንቀሳቃሽ ስልካቸው እንዳይጠለፍ የሚከላከል መሳሪያ ተገጥሞላቸው ነበር፡፡
የአሜሪካው “ፎርብስ” መጽሔት በያዝነው አመት ከአለማችን አስር እጅግ ጠንካራና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ውስጥ በአምስተኛ ደረጃ ያስቀመጣቸው ቻንስለር አንጌላ መርከል፤ ከዚህ ጥንካሬአቸው ባሻገር በቀንደኛ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚነትም በድፍን አውሮፓ ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ይህን ነገረ ስራቸውን ያዩ የሀገራቸው ሰዎች “ዳይ ሀንዲ ካንዝለሪን” ወይም “ባለ ተንቀሳቃሽ ስልኳ መሪ” በሚል የቅጽል ስም ያሽሞነሙኗቸዋል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ቻንስለር አንጌላ መርከል፤ ያለ ተንቀሳቃሽ ስልክ የማይሆንላቸው ሴት ናቸው። ከባለቤታቸው፣ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ከካቢኔና ፓርቲ አባሎቻቸው እንዲሁም ፕሬዚዳንት ኦባማን ከመሳሰሉ የአለም መሪዎች ጋር በዋናነት የሚገናኙት ቢሮዋቸው ውስጥ ባለው ስልክ ሳይሆን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ነው፡፡ በሀገራቸውም ሆነ ከሀገራቸው ውጪ አሰልቺ ወይም ደባሪ ስብሰባ ሲያጋጥማቸው መሠልቸታቸውንና ድብርታቸውን የሚያስወግዱት በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ጌም በመጫወት አሊያም መልዕክት በመላላክ ነው፡፡ የአሜሪካው ብሔራዊ የደህንነት ድርጅት ደግሞ ይሄንን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በርሊን የሚገኘው አዲሱ የአሜሪካ ኤምባሲም አሪፍ የስራ ቦታ ሆኖለታል፡፡ በዚህ ቢሮ ውስጥም እጅግ የተራቀቁ የስለላ መሳሪያዎችን በመትከል፣ የቻንስለር አንጌላ መርከልን የስልክ ንግግርና መልዕክት መጥለፍ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዷን እንቅስቃሴያቸውን ሁሉ በጥብቅ ይከታተል ነበር፡፡
በ2008 ዓ.ም ከፍ ባለ ስነሥርዓት አዲሱን የአሜሪካ ኤምባሲ መርቀው ሲከፍቱ፣ ከአሜሪካ ውጪ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መንጋ የአሜሪካ ሰላይ የሚርመሰመስበት ዋነኛ ጣቢያ ይሆናል ብለው ያልገመቱት ቻንስለር አንጌላ መርከል ብቻ ነበሩ። የማታ ማታ የቅሌቱን ዜና የነገሯቸው የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸው ነበሩ፡፡ ጉዳቸውን ከሀ እስከ ፐ ሰምተው ከጨረሱ በኋላ፣ በከፍተኛ የቁጣ ስሜት “አሀ! እንደ ምስራቅ ጀርመን ጊዜ መሆኑ ነው” አሉ፡፡ አንጌላ መርከል ተወልደው ያደጉት ምስራቅ ጀርመን ውስጥ ስለነበር የኮሙኒስት ፓርቲውን የስልክ ጠለፋ የስለላ ዘዴ በሚገባ ያውቁታል፡፡ ለስርአቱ የነበራቸው ጥላቻ ዛሬም ድረስ አልበረደላቸውም፡፡
ቃል አቀባያቸው ስቴፈን ሲይበርት እንደመሠከሩት፤ አንጌላ መርክል ለፕሬዚዳንት ኦባማ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ደወሉና አይናቸው ላይ በግልጽ የሚታየውን ከፍተኛ የቁጣ ስሜት እንደምንም ተቆጣጥረው “አንተ! ተንቀሳቃሽ ስልኬን ጠልፈህ ስትሠልለኝ ኖረሃል ለካ! ስማ እንዲህ ያለው ወራዳ ድርጊት በመካከላችን ያለውን መተማመን ጨርሶ እንደሚያጠፋው አታውቅም” አሏቸው፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ አስሬ እየማሉና እየተገዘቱ ጉዳዩን አላውቅም አሉ፡፡ የስራ ባልደረቦቻቸውም፤ እርግጥ ነው አንጌላ መርክል ይሰለሉ እንደነበረ ፕሬዚዳንት ኦባማ አያውቁም ነበር አሉላቸው። በመሀሉ ግን የብሔራዊ ደህንነት ድርጅቱን ሃላፊዎች ጠርተው ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ከጠየቁ በኋላ ፕሮግራሙ እንዲገደብ አዘዙ፡፡
የዚህ የስለላ ነገር በአለም አቀፍ ደረጃ ያስነሳው አቧራ፣ የድርጅቱን ሃላፊ ጀነራል ኪዝ አሌክሳንደርን በጣም አብሽቋቸው ነበር፡፡ ኮንግረሱና ሴኔቱ፣ የፖለቲካ ተንታኝ ነን የሚሉት ሁሉ ድርጅቱን የሚከሰቱና ክፉኛ የሚወቅሱት ስለተሰላዮቹ መሪዎች ማወቅ ያለበትን ያህል ማወቅ አልቻለም እያሉ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ትችቱ እንዴት የአጋር አገር መሪዎችን እየሰለለ ሀገሪቱን ቅሌት ያከናንባል ወደሚል ተቀይሯል፡፡ ጀነራል ኪዝ አሌክሳንደር ግን ብሽቀታቸውን ዋጥ አድርገው በመያዝ፣ ለጠየቃቸው አካል ሁሉ በአዋጅ ከተሰጣቸው ተግባርና ሃላፊነት ውጪ አንዳችም ህገወጥ ተግባር እንዳልፈፀሙ፣ መሪዎችን መሠለል ደግሞ ዋነኛው ስራና ሀላፊነታቸው መሆኑን ወዲያና ወዲህ ሳያወላዱ ፈርጠም ብለው አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻ ጽሑፌን የምቋጨው በአንድ ሁነኛ ጥያቄ ነው፡፡ “ለመሆኑ ሌሎችን በመሰል የታወቀው የብሔራዊ የደህንነት ድርጅት የራሱን ምስጢር በወጉ ሸክፎ መያዝ እንዴት አቃተው?”

Published in ከአለም ዙሪያ
Saturday, 02 November 2013 11:28

“አባ ጅራፎ”

አባ ጅራፎ መነኩሴ ናቸው፤ ጅራፍና መስቀል ከእጃቸው ስለማይለይ “አባ ጅራፎ” የሚል ስም ወጥቶላቸዋል፡፡ በእርግጥ ስሙን ማን እንዳወጣላቸው አይታወቅም፤ “እርግጠኛ ስማቸውን አውቃለሁ” የሚል ምዕመንም የለም። በአጠቃላይ አባ ጅራፎ ትክክለኛ ስማቸውም አድራሻቸውም አይታወቅም፡፡ ብቻ ድንገት አንዱ ገዳም ወይም ደብር ይገኙና ይሰብካሉ፤ ምእመናኑን በጠበል ይጠምቃሉ፡፡
በእሳቸው እጅ ከሚጠመቁ በርካታ ምእመናን ውስጥ የማይለፈልፈው ጥቂቱ ብቻ ነው፤ ወይ “ዛር ውላጅ ነኝ” ይላል፤ አለዚያም የሆነ ስም ጠርቶ “ጋኔን” መሆኑን ይናዘዛል፤ በታማሚው ላይ ዳግም እንደማይደርስም በአርባ አራቱ ታቦት ይምል ይገዘታል፡፡ እንዲህ የሚያደርገው ታዲያ የአባ ጅራፎን ጅራፍ እየፈራ ነው፡፡ “አልናገርም” ያለ ተጠማቂ፣ ያ እንደወጨፎ ጥይት የሚጐነው ጅራፋቸው ይቆነዳዋል፡፡ ስለዚህ ሰይጣን ቢኖርበትም ባይኖርበትም፤ ዛር ውላጅ ቢያድርበትም ባያድርበትም ከአባ ጅራፎ ፊት ከጠበል መሃል ራቁቱን ቆሞ የማይለፈልፍ የለም። “ማነህ? ምንድነህ? የት አገኘኸው?” የማይቀሩ የአባ ጅራፎ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ተጠማቂውም የሚያውቀውን የዛር ወይም የሰይጣን ስም እየደረደረ፣ የወንዝ፣ የጫካ አይነት እየሰተረ “ከዚህ” ወይም “ከዚያ እንዲህ ሲያደርግ ያዝሁት” ማለት አለበት፡፡ አለዚያ የአባ ጅራፎ ጅራፍ እንደመብረቅ ድንገት ሊያስገመግም ይችላል፡፡
“ምስህ ምንድነው?” ሌላው የአባ ጅራፎ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የሚቀርበው ግን በተጠማቂው ላይ ያደረው መንፈስ ዛር፣ ወይም ሰይጣን መሆኑ ከታወቀ በኋላ ነው - የመሰነባበቻ ጥያቄ፡፡ ዛሩ ወይም ሰይጣኑ ምሱን ከተናገረ በኋላ ነው ሌላው የምእመኑ ጣጣ የሚቀጥለው፡፡ ተጠማቂው ምእመን ምስ ሲጠየቅ “አተላ፣ የዶሮ ኩስ፣ የአህያ ፋንድያ፣ አመድ” ሌላም” ሊል ይችላል፡፡ መከራው ግን የጠየቀው ምስ ሲቀርብለት ከመመገቡ ላይ ነው፡፡ አንዴ ለፍልፏልና ማንም አይለቀውም፡፡ ስለዚህ ወደደም ጠላ ፋንድያውን ወይም የዶሮውን ኩስ ወይም አመዱን፣ አተላውን መጋትና መገላገል አለበት፡፡
ይህ በጠበሉ በኩል የሚስተዋለው ነው፡፡ በስብከት ረገድም “አባ ጅራፎ አሉ” ከተባለ እንኳን የሰበካው ነዋሪ፣ የጐረቤት አጥቢያ ደብር ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው እንዲያዳምጡ የተወሰነባቸው እስኪመስሉ ድረስ ልጅ አዋቂው፣ ህፃን ሽማግሌው ሳይቀሩ ዙሪያቸውን ይሰበሰቡና አፋቸውንም ጆሮአቸውንም ከፍተው ያዳምጧቸዋል፡፡
“እግዚኦ በይ! ወዮ በይ!” አባ ስብከታቸውን ሁልጊዜ በማስፈራራት ይጀምሩና በማሳቀቅ ይጨርሱታል፡፡
በረጅም ቁመናቸው ከቆዳ የተሰራ አጽፋቸውን (ካባ የሚመስል ቅርጽ ያለው) በላይ ደርበው፣ ከስር ያደፈ ቢጫ አንሶላ ለብሰው፣ እርስ በርሱ ተያይዞ የወለተ ፀጉር በሸፈነው አናታቸው ላይ ጭቅቂት የወረሰው ቆብ ደፍተው፣ ጅራፍና መስቀላቸውን አጣምረው ይዘው ሲታዩ በእርግጥም አባ ጅራፎ አንዳች የሚያስፈራ ነገር ተሸክመው የሚዞሩ ይመስላሉ፡፡
ጥር 18፤ ጐጃም ውስጥ አባዛዥ ጊዮርጊስ ክብረ በዓል ላይ…
“እግዚኦ በይ! ሁልሽም ንስሃ ግቢ! ከወደምስራቅ ክፉ ነፋስ ይነሳል፤ ነፋሱ የዋዛ አይደለም፤ ገለባ አንስቶ እንደሚጠፋ ወይም ደካማዋን ብናኝ እንደሚበትነው ቀላልና ተራ ነፋስ አይደለም፤ ሰማያትን ያናውጣል፤ ምድርን እንደቂጣ ይገለብጣል፤ ተራሮችን እንደ አክርማ ይሰነጥቃል፤ ወንዞችንና ሃይቆችን እንደ ቋንጣ ያደርቃል…” ስብከታቸውን ቀጥለዋል። ብዙው ምእመን ከንፈሩን እየመጠጠ ክፉ ነፋስ እንዳያገኘው በየሆዱ ፈጣሪውን ይለምናል፡፡
ከመሃል አንዱ ተጠራጣሪ “ውሃና ቋንጣን ምን አገኛቸው? ሌላ ምሳሌ አጥተው ነው?” ሲል አጠገቡ ለነበረ ጓደኛው ሹክ አለለት፡፡
“ዝም ብለህ አዳምጥ! እግዚሃር የገለጠላቸውን ነው፤ እሳቸው ምን ያርጉ” ጓደኛው መለሰለት፡፡
“ግን ለምንድን ነው ሁልጊዜ የሚያስፈራሩን?” ተጠራጣሪው መልሶ ጠየቀ፡፡
“የታያቸውን ነው አልሁህ’ኮ! እሳቸው እግዚሃር ሆነው የሚመጣውን መአት አይመልሱት…”
“መጣልሽ! ያው… የመከራው አውሎ ነፋስ እየገሰገሰ ነው፤ ወዮልሽ!…” አባ ጅራፎ የመከራ ምጽአት ስብከታቸውን ቀጠሉ፡፡
“…ጾም የገደፍህ ወዮልህ! ያመነዘርህ ወዮልህ! የዋሸህ፣ የቀጠፍህ ምላስህ ይቆረጣል! በሃሰት የመሰከርህ አንደበትህ ይዘጋል! ነፍስ ያጠፋህ…” አባ ጅራፎ ስብከታቸውን ድንገት አቋረጡና ዙሪያቸውን የከበበውን ህዝብ በስጋትና በፍርሃት ማስተዋል ጀመሩ፡፡ ሁልጊዜም ስለነፍስ ማጥፋት ወንጀል ክፉነት ሲሰብኩ ከምር ይሸበራሉ፡፡ ቢችሉ ቃሉን ባይናገሩት ይመርጣሉ፤ ግን ስብከት ሲጀምሩ የስብከታቸው መሰረቶች አሰርቱ ትእዛዛተ ኦሪትና ስድስቱ ቃላተ ወንጌል በመሆናቸው “አትግደል” የሚለውን ጥብቅ ትእዛዝ ማለፍ አይችሉም፡፡
“ልጆቼ፤ አትግደሉ!” አሉ፤ ሲቃ ቢጤ እየተናነቃቸው፡፡
“አትግደሉ” ድምጻቸው ድክም አለ፡፡
“የሚወዱት የቅርብ ዘመድ በሰው ተገድሎባቸዋል ማለት ነው?” አለ ተጠራጣሪው ሰውዬ ያን ጊዜ ብቻ እያዘነላቸው፡፡
“እሳቸው የሚጠልዩት ለዓለም ነው፤ ምን ዘመድ ይኖራቸዋል” ጓደኛው በሀዘን መለሰለት፡፡
“እሱማ እውነትህን ነው፤ መቸም ሰው ተሰው እንጂ ተሌላ አይፈጠርም ብዬ ነው”
“ቢሆንም ማቄን ጨርቄን ሳይል የመነነ መነኩሴ፤ ለዓለሙ ህዝብ እንጂ ለራሱና
ቤተሰቦቹ አይጨነቅም”
አባ ጅራፎ ስብከታቸውን ቀጠሉ፤ ህዝቡም ያለመታከት እያዳመጣቸው ነው፡፡ አብዛኛው ህዝብ የሚመለከታቸው “ይመጣል” ካሉት የመከራ ወጀቦ እንዲታደጉት በእግዚአብሔር የተላኩ መሲህ አድርጐ ነው፡፡
ዕለቱ ሰማዕቱ ጥር 18 በመሆኑ የሰባር አጽሙን ክብረ በዓል ለመታደምና ከጻድቁ ረድኤት በረከት ለመካፈል የተሰበሰበው ህዝብ የትየለሌ ነው፡፡ መደበኞቹ ሰባክያነ ወንጌልም ሆኑ ተጋባዥ ሰባክያን አውደ ምሕረት ላይ ቆመው ከሚያስተምሩት ይልቅ አባ ጅራፎን ለማዳመጥ ዙሪያቸውን የተሰበሰበው ህዝብ በእጅጉ ይበዛል - የሚታመነው የበቁ፣ የነቁ፣ ምእመናንን ከዲያብሎስ መንጋጋ፣ ከድንገተኛ የመቅሰፍት አደጋ ሊጠብቁ የተላኩ ቅዱስ ተደርገው ነዋ!
“ወዮልህ!”…” አባ ጅራፎ ስብከታቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ የቆሙበት ቦታ ጉብታ ስለሆነ ለሁሉም በደንብ ይታያሉ፡፡
“ዘንዶው ይመጣል፤ ሰውን ብቻ አይደለም ዕጸዋትን አዕባንን እንደ ቅቤ ይውጣል፡፡ በዚያ ጊዜ ሰው ሆኖ ያልተፈጠረ ምንኛ የተባረከ ነው!”
“ድንጋዩንም እንጨቱንም ዘንዶው የሚውጠው ከሆነ ሰው ሆኖ አለመፈጠር ምን ጥቅም አለው?” ተጠራጣሪው ሰውዬ ጓደኛውን ጠየቀው፡፡
“ዝም በል እባክህ ልስማበት! የዘመኑን ክፋት፣ የሃጢአታችንን ብዛት በምሳሌ እየነገሩን እኮ ነው” ጓደኛው መለሰ፡፡
“ዘጠኝ ሞት መጣ ቢለው አንዱን ግባ በለው” አለ አሉ የአገሬ ሟች፤ አንድ ጊዜ አውሎ ነፋስ፤ አንድ ጊዜ ዘንዶ፤ ሞት ካልቀረ ምን ያስጨንቀኛል?”
“ንስሐ ግቡ ብለዋል’ኮ፤ ንስሐ ከገባን ቢያንስ ሞታችን የክፉ ሞት፣ የስቃይ ሞት አይሆንም” ጓደኛው በለሆሳስ መለሰ፡፡
“ፍካሬ ኢየሱስ እንዲህ ይላል፤ የመጨረሻው ቀን ሲመጣ ህዝብ በህዝብ ላይ፣ ንጉሥ በንጉሥ ላይ ይነሳል” ተጠራጣሪው ሰውዬ ሳቁ መጣ፡፡ “ምን ንጉሥ አለና በሌላ ንጉሥ ላይ ይነሳል? ሸህ ጅብሪል” የሚባሉ ወሎዬ ያሉትን አያውቁም ማለት ነው?”
“ምን አሉ?”
“ግባ በቀላጤ፣ ውጣ በቀላጤ፤
ከተፈሪ ወዲያ አይባልም አጤ ”ተፈሪ ማለት አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው”
“ገጣሚው ሸህ ናቸው አይደል?”
“አዎ”
“ታዲያ አባ ጅራፎኮ መናኝ መነኩሴ ናቸው፤ አንተ ከምትላቸው ሸህ እሳቸው አይበልጡም?”
“ሁሉም በየቤቱ ትልቅ ነው፤ እግዜር አመለከተኝ ነው የሚል” ጓደኛሞቹ በሸክሹክታ ማውራታቸውን ሲያዳምጥ የነበረ ሶስተኛ ሰው ዝም እንዲሉ ገሰፃቸው።
“አባት በልጁ፤ ልጅ በአባቱ ላይ ይነሳል፤ ሁሉም ቤቱን ይገነባል፤ ግን አይኖርበትም፡፡ በየመንደሩ ሹመት ይበዛል፣ ግን መደማመጥ የለም” አባ ጅራፎ ስብከታቸውን ገፉበት፡፡
“በየመንደሩ ሹመት ይበዛል” ያሉትኮ ቀበሌን ነው፤ እውነታቸውንኮ ነው፡፡
ቀበሌ ማንን ያዳምጣል? የቀበሌን ስልጣንስ ማን ከቁብ ይቆጥረዋል?” የተጠራጣሪው ጓደኛ በመገረም አስተያየቱን ለገሰ፡፡
“በያገሩ የምድር መናወጽ ይሆናል፤ ራብ ቸነፈር ይበዛል፤ አስረሽ ምቺው የየሰው የዕለት ተዕለት ተግባር ይሆናል፤ በዚህም እግዚአብሔር ፊቱን ከህዝቡ ያዞራል…” አባ ስብከታቸውን ቀጥለው ሳለ፣ ድንገት የተሰማ ከፍተኛ ጩኸት አቋረጣቸው፡፡
“ራሱ ነው! ይህን መልቲ ያዙልኝ! ጐበዝ በጻድቁ ይዣችኋለሁ፤ እንዳትለቁት!” ከህዝቡ መሃል እንደ እብድ የሚጮኸው ሰውዬ ፊት ለፊቱ ያገኘውን ሁሉ እየገፈተረ ወደ አባ ጅራፎ መገስገሱን ቀጠለ፡፡
“እብድ ነው! ያዙት!” የብዙ ሰው ድምጽ ደጋግሞ አስተጋባ፡፡ ሰውየው ግን ሊቆም አልቻለም፡፡
“ይህን ነፍሰ ጉዳይ ያዙልኝ! መነኩሴ አይደለም ሲያታልል ነው፡፡ የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ታላቅ ወንድሜን ገድሎ ሲታደን የኖረ ወንጀለኛ ነው ያዙልኝ!” አይኑን አፍጥጦ ወደ አባ ጅራፎ ገሰገሰ፡፡ ንግግሩን የሚያዳምጠው ሁሉ “በእርግጥም እብድ ነው” ብሎ አሰበ፡፡
አንዳንዶች ብቻ አባ ጅራፎንም የሰውየውን ንግግርም እኩል ጠረጠሩ፡፡
“አንት ጭራቅ አገኘሁህ! ወንድሜን እንደበላኸው አልቀረህም” ብሎ ዱላውን መዝዞ ወደ አባ ጅራፎ ሲጠጋ፣ መስቀላቸውን ወደ ኪሳቸው አስገቡ፤ በዚያው ቅጽበት በአጽፋቸው ውስጥ ደብቀውት የነበረውን ፍሻሌ ሽጉጥ አወጡና የሰውየውን ግንባር እንደ አክርማ ለሁለት ሰነጠቁት፡፡

Published in ልብ-ወለድ

አቶ ዘሪሁን አበበ ይግዛው ይባላሉ፡፡ የአባይን የውሀ ፖለቲካና የታላቁን ህዳሴ ግድብ ማዕከል አድርጐ ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት የተቋቋመው “የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ባለሙያዎች ድጋፍ ለአባይ” ማህበር የህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ሀላፊ ናቸው፡፡ የዛሬ አራት ወራት የተቋቋመው የሙያተኞች ማህበር እንዴት እንደተመሰረተ፣ ስለተመሰረተበት አላማ፣ ማህበሩ እስካሁን ስለተንቀሳቀሰባቸው ጉዳዮች፣ ስለ መስራቾቹና ስለ ወደፊት እቅዶቹ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአቶ ዘሪሁን አበበ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡ አቶ ዘሪሁን አበበ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስና በአለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ያገኙ ሲሆን የማስተርስ ዲግሪያቸውን በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ከስዊዘርላንድ ጄኔቫ አግኝተዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግባርና የስነ ዜጋ መምህር ናቸው፡፡

“አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ማህበር ለአባይ” (Ethiopian International Professional-support for Abay) (EIPSA) የተባለው ማህበር መቼና በማን ተቋቋመ?
EIPSA (ኢፕሳ) በሚል ምህፃረ-ቃል የምንጠራው ማህበር የተቋቋመው፣ በጁን 22 ቀን 2013 ዓ.ም ነው፡፡ ፅንሰ ሀሳቡን በዋናነት ያመነጩት ዶ/ር በላቸው ጨከነ ከለንደን እና ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ ከካናዳ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉት ምሁራን ያላቸውን የግንኙነት መረብ በመጠቀም የተለያዩ በውሀ መስክ ላይ የሚሰሩ ምሁራንን፣ የህግ ባለሙያዎችን፣ የአለም አቀፍ ግንኙነት የፖለቲካ ተንታኞችን፣ የዩኒቨርስቲ መምህራንን፣ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚወክሉ ግለሰቦችን፣ በተለያዩ የአለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በመሰብሰብ መስራች ጉባኤ ተካሄደ፡፡
የት ነው መስራች ጉባኤው የተካሄደው?
መስራች ጉባኤው የተካሄደው በያለንበት አገር “ስካይፒ” በመጠቀም ነው፡፡ ለሚመለከታቸው ከ15-20 ለሚደርሱ ሰዎች ጥሪ ተደረገ፡፡ 15 ያህል ሰዎች ተገኝተው ኢፕሳ ተመሰረተ፡፡ በኋላ ግን ጋዜጣዊ መግለጫ በማውጣት፣ በመላው አለም ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ጥሪ ተደረገ፡፡ ከ67% በላይ የሆኑ የማስተርስ ዲግሪ ምሩቃን፣ ከ17-20 በመቶ የሚሆኑ ፒኤችዲያቸውን በተለያየ መስክ የሰሩ ፕሮፌሰሮችና እንዲሁም በተለያየ ዘርፍ ጥናት የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በማሰባሰብ የተቋቋመ የሙያተኞች ማህበር ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ምን ያህል አባላት አሉት?
እውነት ለመናገር ማህበሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳዲስ አባላትን እያካተተ ነው፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከመላው አለም የተውጣጡ ወደ መቶ ያህል አባላት አሉት፡፡
በማህበሩ ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊነቱን ወስደው እየሰሩ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ በምሰረታው ጊዜ ነበሩ?
እኔ በወቅቱ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ነበርኩኝ፡፡ የድህረ ምረቃ ትምህርቴን እየተከታተልኩኝ ነበር፡፡ ያኔ የማስተርስ ተማሪ ነበርኩኝ፡፡
የዚህ ማህበር አባል እንድትሆን ማን ነው ያነሳሳህ?
አስቴር አስገዶም ትባላለች፡፡ ስዊድን ነው የምትኖረው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ናት። ጉዳዩን ከህግም ከሳይንስም አንፃር የምታይ ስትሆን ከስዊድን መንግስት ጋር ነው የምትሰራው፡፡ እርሷ ጠቁማኝ አባል ሆንኩና መስራች ጉባኤውን አካሄድን፡፡
ማህበሩ የተቋቋመባቸውን ዋና ዋና አላማዎች ብታብራራልኝ ….
ማህበሩ የተቋቋመባቸው ከአምስት ያላነሱ አበይት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን ያማከለ የባለሙያዎች ጥምረት (መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት) ከዚህ በፊት አልተቋቋመም፡፡ ሁለተኛው እና ዋናው፤ አለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ግብፃዊያን (ህዝቡ) የሚያውቁት፣ ግብፃዊያን ምሁራን የሚነግሯቸውን እንጂ እውነታውን አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህንን እውነታ ማሳወቅና የአለም አቀፉን ማህበረሰብ አመለካከት መቀየር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ፣ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም የአባይ ተፋሰስ አገራት ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ ፎረም ያስፈልጋል ብለን አምነን የተነሳን ሲሆን ፎረም ሲኖር የሀሳብ መለዋወጥ ይኖራል፤ ትብብርን ማጠናከር ይቻላል ከሚል እሳቤ ነው፡፡ አራተኛው፣ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበትና የሚገናኙበት የራሳቸው የሆነ የጋራ መድረክ ስላልነበራቸው እሱን መፍጠር አስፈላጊ ነበር፡፡ አምስተኛው ጉዳይ፣ ከታላቁ የአባይ ግድብ አንፃር የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ባልሆኑ የሌሎች አገር ዜጐች፡፡ የግድቡን መጠን፣ የሚገደብበትን ቦታና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ማለት ነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በኢትዮጵያዊያን ምሁራን ለመመለስ ታስቦ የተቋቋመ ማህበር ነው፡፡
ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የማህበሩ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ማህበሩ የተለያዩ የራሱ እሴቶች አሉት። በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ማህበር እንደመሆኑ፣ የተለያዩ ምሁራንና ተመራማሪዎች ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱት ግድቡን ነው፡፡ ማህበሩ፤ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የምትሰራቸውን ማናቸውም ፕሮጀክቶች (በፖሊሲ ጥናት ሊሆን ይችላል) ላይ ከተለያየ አቅጣጫ እገዛ ለማድረግ የተቋቋመ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን አባላትን የማሰባሰብና የማደራጀት ሥራ እያከናወነ ነው፡፡
መቀመጫውን ለንደን ያደረገ ማህበር ነውና የማህበሩ አመሰራረት በምን ዘርፍ ነው?
እንዳልሽው መቀመጫው እንግሊዝ ለንደን ውስጥ ነው፡፡ የማህበሩ አመሰራረት ዘርፍ በበጐ አድራጐት ስራ ነው፡፡ በእንግሊዝ ህግ መሰረት እንዲህ አይነት ማህበር ሊቋቋም የሚችለው በዋናነት በበጐ አድራጐት ማህበርነት ነው፡፡ እስካሁን የተሰራው የማህበሩን እግር የመትከል ስራ ነው፡፡ በተጨማሪም የኢፕሳ አባላት ከአባይ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጽሑፎችን ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር ዘርአይ ይህደጐ የሚባሉና በስኮትላንድ አበርዲን ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩ ምሁር፤ ሶስት የተለያዩ ጽሑፎችን ከአለም አቀፍ ህግ አንፃር የግድቡ ሁኔታ እንዴት እንደሚታይ ጽፈዋል፡፡ እኔም ግብፃዊያን ምሁራን የሚጽፏቸውንና አባይን የተመለከቱ ጉዳዮችን በተመለከተ በግብጽ ጋዜጦች ለሚወጡ ጽሑፎች ምላሽ የሚሆኑ ትንታኔዎችን ጽፌያለሁ፡፡ ካይሮ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ምሁርና የማህበሩ አባልም እንዲሁ በ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣና በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ጽፈዋል፡፡ እንዲህ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ናቸው፡፡
ማህበሩ የራሱን ድረ ገጽ አዘጋጅቷል፡፡ በቅርቡ ከፍቶ ከግድቡና ከአባይ ውሃ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን መረጃ ወደ መረጃ ቋቱ ያፈሳል፡፡ በሌላ በኩል ዋና ዋና እቅዶች አሉት ማህበሩ፡፡ ጥናታዊ ጽሑፎችን ማዘጋጀት፣ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ማዘጋጀትና የህዳሴው ግድብ የሚገነባበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድረስ በመሄድ ማንኛውም አይነት የሙያ እገዛ ማድረግ ይገኙበታል፡፡ አባላቱ ከአለም አቀፍ ፖለቲካ፣ ከምህንድስና፣ ከአካባቢ ጥበቃና ከመሳሰሉት ባለሙያዎች የተውጣጡ ስለሆነ በእነዚህ ዘርፎች የተለያዩ ስራዎችን ለማከናወን አቅደናል፡፡ በዚህም መንገድ በአባይና በግድቡ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንችላለን፡፡
ሌላው የሰራው ነገር፣ ከብሔራዊ የግድቡ አስተባባሪ ጽ/ቤት ጋር ግንኙነት መስርተናል፡፡ ከተለያዩ ተቋማት ለምሳሌ ከመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ጋር በመደበኛም መደበኛ ባልሆነም መልኩ ግንኙነት ተመስርቷል፡፡
ከኢትዮጵያዊያን ምሁራን በፊት በካይሮ ዩኒቨርስቲ “የአባይ ቡድን” (Group of the Nile) የተባለ የምሁራን ማህበር ተመስርቶ የአባይና የህዳሴ ግድብ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አውቃለሁ። “ኢፕሳ” ከግብፃዊያን አይቶ ነው የተመሰረተው ይባላል፡፡ እስቲ ስለ ናይል ቡድን እና በእንቅስቃሴው ዙሪያ ያለህን መረጃ ንገረኝ …
እንዳልሽው ነው፤ “የናይል ቡድን” በካይሮ ዩኒቨርስቲ ከተለያየ የሙያ ዘርፍ የተቋቋመ ነው፡፡ ከመስኖ ምህንድስና፣ ከአካባቢ ጥበቃና ከመሳሰሉት የተውጣጡ ሙያተኞች ስብስብ ነው። በአጋጣሚ ይሁን ወይም ታስቦበት የአባይ ግሩፕ የሚባለው ስብስብ የቀድሞውን የውሃና የመስኖ ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ነስረዲን አለንአለምን ያካተተ ነው። በነገራችን ላይ ይሄ ቡድን እስካሁን አንድ ጽሑፍ ነው ያወጣው፡፡ እንደምታውቂው የተቋቋመው ኢትዮጵያ ግድብ መገንባቷን ተከትሎ ነው፡፡ ይህ ቡድን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እና ኢትዮጵያ ልትሰራቸው ያሰበቻቸው ሌሎች አራት ግድቦች ማለትም፡- ቤኮ አቦ፣ ናካራዶቢ እና ሌሎች ሁለት ግድቦችን መሰረት በማድረግ አንድ ጽሑፍ አውጥተዋል፡፡
ያ ጽሑፍ ግን የሚያጠነጥነው በአንድ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ የቀድሞ የ1959 ስምምነት እንዳይነካ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ የአለም አቀፍን ህግ ስንመለከት፤ ያ ህግ (ስምምነት) ዋጋ የለውም፤ ምክንያቱም ሌሎቹን ዘጠኙን የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ከአባይ ጋር የተያያዘ ብሔራዊ ጥቅም በትክክል ያገናዘበ አይደለም፡፡ ሌላው አለም አቀፍ ሙያተኞች ያወጡትን ሪፖርት ተከትሎ ፅሁፍ አዘጋጅተዋል። እነሱ በዋናነት የህዳሴው ግድብ መጠን ማነስ አለበት፤ ምክንያቱም ብዙ ውሃ ይይዛል የሚል ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ጽሑፉ ቢወጣም መሰረተ-ቢስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከምን አንፃር ነው ግድቡ የሚያንሰው የሚለውን ምክንያታቸውን ስናይ፣ ኢትዮጵያ የግብፅ የውሀ ዋስትናን ይዛ ታስቀራለች የሚል ነው፡፡ እነሱ የሚያነሱት የውሀ ዋስትና (Water Security) ፅንሰ ሀሳብ በውል ያልተተነተነ፣ በተለያየ ዘርፍ ያሉ ምሁራን ስምምነት ላይ ያልደረሱበት አሻሚ ፅንስ ሀሳብ ነው፤ ይሁን እንጂ ዞሮ የሚጠጋው ወደ 1959ኙ ስምምነት ስለሆነ፣ ያንን እንድትቀበል ኢትዮጵያን ለመገፋፋት መንግስታቸውን የማነሳሳት ስራ ነው የሚሰሩት፡፡ ያ ደግሞ ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም ለዚህ መልስ የሚሆን ፅሁፍ አዘጋጅቼ ለአንባቢያን አብቅቻለሁ፡፡
እስኪ የማህበራችሁ አወቃቀር ምን እንደሚመስል አብራራኝ …
ኢፕሳ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አለው፡፡ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው 10 አባላት አሉት፡፡ ከአስሩ አንዱ ጀነራል ዳይሬክተሩ ነው፡፡ ዋና ፀሀፊ አለው። የፋይናንስ ጉዳዮችን የሚመለከት አንድ ክፍል አለ። እዚህ ውስጥ ሰባት ዲፓርትመንቶች አሉ፡፡ ከሰባቱ አንደኛው የምህንድስና ክፍል ሲሆን ሁለተኛው የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ክፍል ነው፡፡ ሶስተኛው የአለም አቀፍ ህግና የአለም አቀፍ ጉዳዮች ክፍል ነው። አራተኛው የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ነው፡፡ አሁን እኔ በሃላፊነት የምመራው ክፍል ማለት ነው፡፡ አምስተኛው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ነው፡፡ ስድስተኛ የምጣኔ ሀብት ክፍል አለ። በዋናነት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ማስተባበሪያ አስተዳደር ክፍልም አለ፡፡ በዚህ አወቃቀር ነው የተመሰረተው፡፡
በአሁኑ ሰዓት “ኢፕሳ”ን በዳይሬክተርነት የሚመሩት ማን ናቸው?
ዋና ዳይሬክተራችን ዶ/ር በላቸው ጨከነ ይባላሉ፡፡ ለንደን ነው የሚኖሩት፡፡ ዋና ፀሀፊያችን ደግሞ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ ናቸው፤ ካናዳ ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ማህበሩ እንዲመሰረት ሀሳብ ያመነጩም ናቸው፡፡
የማህበሩ አባላት ግድቡን ጐብኝተዋል?
እንደ አጋጣሚ ሆኖ አብዛኛዎቹ የማህበሩ አባላት የሚኖሩት በተለያዩ የአለም አገራት ነው። በመሆኑም ወደ ግድቡ እስካሁን የሄደ የለም፡፡ ሆኖም በቅርቡ አንዲት አባላችን ከእንግሊዝ ትመጣለች፡፡ ዶ/ር ምንትዋብ ትባላለች፡፡ ዶ/ር ምንትዋብ በዋናነት የምትመራው የምጣኔ ሀብት ክፍሉን ነው፡፡ እኔም እሷም ተነጋግረን አንዳንድ ነገሮችን ለማድረግ አስበናል፤ ነገር ግን በዋናነት ዌብሳይቱ በይፋ ስራ ከጀመረ በኋላ ዳይሬክተሩን፣ ዋና ፀሀፊውን እና ሌሎች አባላትን ጨምረን በግድቡ ዙሪያ ጥናት ለመስራትና በአካል ለመጐብኘት እቅድ ተይዟል፡፡
የማህበሩ የገቢ ምንጭ ምንድን ነው?
እስካሁን ማህበሩ ለሚያስፈልገው አንዳንድ ወጪ አባላት ከኪሳቸው ነው የሚያወጡት፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ማህበሩ በበጐ ፈቃደኝነት እና በበጐ ፈቃደኞች የተመሰረተ ነው፡፡ ነገር ግን አንዱ የአባልነት ግዴታ ምንድን ነው? በተቻለ መጠን ድጋፍ የሚያደርግና የተወሰነ ወጪ የሚሸፍን መሆን አለበት ነው፡፡ እስካሁን ሌላ ገቢ የለውም። ያው አባላት ከኪሳቸው በሚያወጡት ገንዘብ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ አሁን ማህበሩ ከተመሰረተ አራተኛ ወሩን ይዟል፡፡
አባላቱ ከሙያቸው ውጭ ሌላ ምን ድጋፍ ይሰጣሉ? ለምሳሌ የፋይናንስ ድጋፍን በተመለከተ ምን ያስባሉ?
ማህበሩ የባለሙያዎች ስብስብ ነው፡፡ ስያሜውም ይህን ነው የሚገልፀው “የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ባለሙያዎች ድጋፍ ለአባይ” ነው የሚሰኘው፡፡ ትኩረት ያደረገውም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ እንደመሆኑ፣ በጐ አድራጐት ድርጅቱ ሙያዊ ድጋፍ ነው የሚያደርገው፡፡
ለምሳሌ ጥናታዊ ፅሁፎችን ይሰራል፡፡ አገሪቱ የሰለጠነ ባለሙያ እንዲኖራት የማድረግ አላማን የሰነቀም በመሆኑ የስኮላርሽፕ እድሎችን በማመቻቸት እና ወጣት ምሁራን የምዕራባዊያኑን ልምድ እንዲቀስሙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ እንዲህ እንዲህ አይነት ድጋፎችን ይሰጣል፡፡ የንዘብ ድጋፍን በተመለከተ እስካሁን የታሰበ ነገር የለም፡፡ ማህበሩ በቀጣይ የልቀት ማዕከል (Center of Excellence) መሆን ይፈልጋል፡፡ ወደ ልቀት ማዕከልነት ሲያድግ፣ አገሪቷ የምታደርጋቸው ማንኛውም ከውሃ ጋር የተያያዘ እንቅስቃሴ ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለፖሊሲ አውጭ አካላት ድጋፍ ማድረግ፣ እውቀት ለሚሹ አካላትም እንዲሁ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይቀጥላል፡፡
ማህበሩ ሲቋቋም ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ያገኛችሁት ምላሽ ምን ይመስላል?
ከመንግስት በኩል ደስ የሚል ምላሽ ነው ያገኘነው፤ ምክንያቱም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ የመንግስት ፕሮጀክት ብቻ አይደለም፡፡ የአገር ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን፣ ኢትዮጵያዊያንን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የሚቀጥል በመሆኑ፣ ከብሔራዊ የግድቡ አስተባባሪ ኮሚቴም ሆነ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጐ የሆነ ምላሽና አብሮ የመስራትም አዝማሚያ ታይቷል፡፡
በግብጽ ካይሮ ዩኒቨርስቲ የተቋቋመው የናይል ቡድንም ሆነ የኢፕሳ ምሁራን ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው ህዝቡን ለማሳመንና በጋራ ጥቅም ላይ ተስማምቶ ለመስራት ምን ያሰባችሁትን ነገር አለ?
ኢፕሳ ሲቋቋም በዋናነት ይዞ የተነሳው አቋም፣ አለምአቀፍ ህግጋትንና መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አንፃር የተለያዩ ህጐች አሉ፡፡ የተቋቋመበት አላማና አካሄዱ ግን አለምአቀፍ መርሆ ነው፡፡ ያ አለም አቀፍ መርሆ ደግሞ ፍትሀዊና ምክንያታዊ የሀብት ክፍፍል እና የውሃ አጠቃቀምን መሰረት አድርጐ የተነሳ ነው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የካይሮ የናይል ግሩፕና የኢትዮጵያው ኢፕሳ የሚያራምዱት አቋም በዓለም አቀፍ ህግጋት ስናየው ግራና ቀኝ የሚቆም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምታራምደውና ኢፕሳ የሚያራምደው አቋም ግን አንድ የአለም አቀፍ ህግን መሰረት ያደረገና ተቀባይነት ያለው ገዢ ሃሳብ ነው፡፡ ማህበራችን በአገራት መካከል ግንኙነት መጠንከር አለበት ይላል፡፡ እያንዳንዱ የተፋሰሱ ሀገራት አባይን ፍትሀዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብት አለው፤ ይህ በአለም አቀፍ ህግ የተደነገገ ነው። ስለዚህ ኢፕሳ ከማንኛውም የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ከ460 ሚሊዮን በላይ የሆኑ በአባይ ተፋሰስ ለሚኖሩ ህዝቦች ተጠቃሚ ማድረግ ዓላማው ነው፡፡ አሁን ካለው የአለም የሙቀት መጨመርና ሌሎች ችግሮች አንፃር አገራት ተስማምተው መስራታቸው የአማራጭ ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር የተፋሰሱ አገራት የአባይን ውሃ መጠቀም ያለባቸው ፍትሀዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ነው፡፡ ኢፕሳ ይህን መሰረት አድርጐ ይንቀሳቀሳል። ስለሆነም ወደፊት ከካይሮው የናይል ቡድን ጋር አብሮ የመስራት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ከአፍሪካ የተገኘው አንድ ሃያል ብቻ ነው
ከ72 ሃያላን መካከል ሴቶች 9 ብቻ ናቸው
የቭላድሚር ፑቲን አንደኛ መባል አነጋጋሪ ሆኗል

ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የራሱን መምረጫ መስፈርት ተጠቅሞ፣ ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ በመቶ ሚሊዮን አንድ ሃያል ስሌት የአለማችንን ሃያላን በየአመቱ መምረጥ የጀመረው እ.ኤ.አ በ2009 ነው፡፡
መጽሄቱ እየተገባደደ ባለው 2013 በተሰማሩበት የሙያ መስክ ተጽዕኖ መፍጠር ችለዋል ያላቸውን የአለማችን ሃያላን ግለሰቦች ዝርዝር ለአምስተኛ ጊዜ በዚህ ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡
‘ግለሰቦቹ በምን ያህል ሰው ላይ ሃይላቸውን ማሳረፍ ይችላሉ?’፣ ‘በስራቸው ምን ያህል ገንዘብ ይንቀሳቀሳል?’፣ ‘ከአንድ የሞያ መስክ በላይ ተጽዕኖ መፍጠር ይችላሉ?’ እንዲሁም ‘ተሰሚነታቸውንና ያላቸውን አቅም በመጠቀም አለምን ለመለወጥ ምን ያህል በንቃት ተንቀሳቅሰዋል?’ የሚሉት፣ የፎርብስ ሃያላንን መምረጫ መስፈርቶች ናቸው፡፡
እነዚህን መስፈርቶች በመጠቀም ነው፣ ፎርብስ 7.2 ቢሊዮን ከሚደርሰው የአለም ህዝብ፣ የአመቱ ሃያላን ያላቸውን 72 ግለሰቦች ዝርዝር ይፋ ያደረገው፡፡
በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩስያውን ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲንን ያካተተውና የአመቱ ሃያላን ፊታውራሪ በማድረግ ከፊት ያሰለፈው ይህ ዝርዝር፣ ባራክ ሁሴን ኦባማን በማስከተል የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ዢ ጂንፒንግን በሶስተኛነት አስቀምጧል፡፡
ፎርብስ በአገራቸው ፖለቲካ የነበራቸውን ስልጣን ለማጠናከርና በአለማቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተደማጭነት ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረትና ስኬት በማየት በቀዳሚነት አስቀምጫቸዋለሁ ያላቸው ብላድሚር ፑቲን፣ በብዙዎች ዘንድ ለዚህ ወግ አይመጥኑም የሚል ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ የዘገባውን መውጣት ተከትሎ፣ ፑቲን የሃያላን ቁንጮ ተደርገው ከፊት መቀመጣቸው በተለያዩ የአለም መገናኛ ብዙሃንና በድረ-ገጽ አግባብ አለመሆኑ እየተዘገበና የመነጋገሪያ ርዕስ እየሆነ መጥቷል፡፡ ፎርብስንም ያሳማው ይዟል፡፡
ከ2010 በስተቀር ላለፉት አራት አመታት የፎርብስ ሃያላን ቁንጮ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ባራክ ሁሴን ኦባማ፣ በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው ጅማሬ አንዳንድ የሚያሳሙ ችግሮች ታይተውባቸዋል በሚል በዘንድሮው ዝርዝር አንድ ደረጃ ዝቅ ተደርገዋል፡፡
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳስ ፍራንሲስ፣ የጀርመኗ መራሄ መንግስት አንጌላ መርኬል፣ ቢል ጌትስ፣ የአሜሪካ ፌደራል ሪዘርቭ ዋና ጸሃፊ ቤን ቤርናንኬ፣ የሳኡዲ አረቢያው ንጉስ አብዱላህ ቢን አብዱል አዚዝ አል ሳዑድ፣ የአውሮፓ ሴንትራል ባንክ ፕሬዚደንት ማሪዮ ድራጊ እና የዎልማርት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚካኤል ዱክ ከ4ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡በፎርብስ የአመቱ ምርጥ የአለማችን ሃያላን ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ የአገር መሪዎች፣ የትርፋማ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚዎችና አስተዳዳሪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች፣ በጎ አድራጊዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዳይሬክተሮች፣ ስራ ፈጣሪዎችና ቢሊየነሮች ተካተዋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር ውስጥ የሮማውን ጳጳስ ፍራንሲስ፣ የሳምሰንግ ስራአስኪያጁን ሊ ኩንሂ፣ የኒዮርክ ታይምስ ዋና አዘጋጁን ጂል አብራምሰንና የቮልስ ዋገን ግሩፕ ሊቀመንበሩን ማርቲን ዊንተርኮርንን ጨምሮ 13 አዳዲስ ሃያላን በአዲስ ገቢነት ተካተዋል፡፡
በሃያላኑ ሰልፍ ውስጥ የሴቶች ድርሻና ደረጃ ከአመት አመት እያደገ እንደመጣ የሚያመለክተው የፎርብስ ዝርዝር፣ ከአለም ህዝብ ቁጥር ግማሽ ያህል ከሆኑት ሴቶች መካከል ተመርጠው በዘንድሮው የሃያላን ሰልፍ ውስጥ የገቡት 9 መሆናቸውንና የሃያላኑን 12 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን ያሳያል፡፡
ከእነዚህ የዘንድሮ ሃያላን ሴቶች መካከል የጀርመኗ መራሄ መንግስት አንጌላ መርኬል(5ኛ)፣ የህንድ ብሄራዊ ኮንግረስ ፕሬዚደንት ሶኒያ ጋንዲ(21ኛ) እና የአይ ኤም ኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርዲ(35ኛ) ይጠቀሳሉ፡፡
ፎርብስ በዘንድሮው የሃያላን ዝርዝር ውስጥ 26 የአለማችን ታዋቂ ቢሊየነሮችን ቢያካትትም፣ ለአብዛኞቹ ባለጸጎች የሃያልነት ክብር ያጎናጸፈው ያካበቱትን ሃብት ብቻ ሳይሆን በበጎ ምግባር ስራ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ገልጧል፡፡
ያካበቱትንም የመጸወቱትንም በመገምገም ሃያል ብሎ ከመረጣቸው ቢሊየነሮች መካከል፣ ዋረን ቡፌት(13ኛ)፣ ሚካኤል ብሉምበርግ(29ኛ)፣ ሊ ካሺንግ(30ኛ) እና ሞማመድ ኢብራሂም(71ኛ) የሚጠቀሱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አራቱ ቻይናውያን፣ አራቱ ደግሞ ህንዳውያን ናቸው፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት ቢሊየነሮች የሃብት መጠን አጠቃላይ ድምር፣ ከ564 ቢሊየን ዶላር በላይ መሆኑንና ይህም ከስዊድን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት እንደሚበልጥ፣ የአለም ባንክን መረጃ በመጥቀስ ፎርብስ ዘግቧል፡፡
መጽሄቱ በስራ ፈጠራ መስክ ተጠቃሽ ስራ ሰርተዋል ብሎ በዝርዝሩ ውስጥ ካካተታቸው 12 ግለሰቦች መካከል፣ የጎግል መስራቾች ላሪ ፔጅና ሰርጂ ብሪን(17ኛ)፣ የስፔስ ኤክስፕሎሬሽን ቴክኖሎጂስ ኮርፖሬሽን መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤለን ሙስክ እና ከዘንድሮ ሃያላን በእድሜ ለጋ ተብሎ የተጠቀሰው የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ(24ኛ) ይጠቀሳሉ። አብዛኞቹን ሃያላን ከሰሜን አሜሪካ፣ እስያና አውሮፓ አገራት የመረጠው ፎርብስ ወደ አፍሪካ ፊቱን ሲያዞር ከአንድ ሃያል በቀር አልታየውም፡፡
“አገሬን በወጉ እየመራሁ ነው፣ ህዝቤን የዲሞክራሲ ተጠቃሚ እያደረግሁ ነው፣ ስልጣኔን በአግባቡ እየተጠቀምኩ ነው” እያሉ ምለው ከሚገዘቱ ሃምሳ ምናምን የአፍሪካ መሪዎች መካከል፣ አንዳቸውም የፎርብስን ሚዛን አልደፉም፡፡
“ስራ ፈጣሪ ዜጎችን አፍርተናል” ብለው ከሚመጻደቁ የአፍሪካ አገራት ዜጎች መካከል፣ ለስም እንኳን የፎርብስን ቀልብ የገዛና የሃያልነትን ክብር ሊጎናጸፍ የታደለ ስራ ፈጣሪ አልተገኘም፡፡ ‘በጎ ስራ ሰርተናል’ ብለው በአደባባይ ድምጻቸውን ጎላ አድርገው ከሚያሰሙ ህልቆ መሳፍርት የአፍሪካ መንግስትታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዳይሬክተሮች፣ ፎርቢስ ለአንዳቸውም ጆሮ አልሰጠም፡፡ አንዳቸውንም አልመረጠም፡፡
‘ሃያላን ልጆች እንዳትወልድ የተረገመች አህጉር’ ተብላ ከመታማት ያዳናት የአፍሪካ ብቸኛ የቁርጥ ቀን ልጅ፣ እንደምንም በፎርብስ አይን ውስጥ የገባው ‘አንድ ለአህጉሩ’ ዳንጎቴ ነው - የዳንጎቴ ግሩፕ ኩባንያ መስራች ናይጀሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ(64ኛ)።

Published in ህብረተሰብ

“ሀረስቱል ሽባበል ሙጃህዲን ፊ ቢላደል ሂጅራተይታን” በሚል ስያሜ ተደራጅተው ከአልቃኢዳ አልሸባብ ጋር የቀጥታ ግንኙነት በመመስረ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ የሽብር መዋቅሮችን በመፍጠር ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ ተንቀሳቅሰዋል በሚል በተከሰሱት 28 ግለሰቦች ላይ ምስክሮች እየተሰሙ ነው፡፡
ከጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ የስራ ቀናት ከ40 በላይ የሚሆኑ ምስክሮች በልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ይሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመጀመሪያዎቹ ቀናት ተከሣሾች በተጠርጣሪነት ሲያዙ የአይን እማኝ የነበሩ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የተሰሙ ሲሆን ቀሪ ምስክሮችም መሰማታቸው ይቀጥላል፡፡
በእነ አማን አሠፋ መዝገብ ስር የተካተቱት 28 ተከሳሾች፤ የአልቃኢዳ አልሸባብ የሽብር ህዋስ ነው በተባለው ስብስብ ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነቶችና አባልነት የተሳተፉ መሆናቸው በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ተመልክቷል፡፡
በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበው ጥቅል ክስ እንደሚያስረዳው፤ ግለሰቦቹ የወንጀሉ ዋና ተሳታፊና ፈፃሚ በመሆን ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማፍረስ በሼሪያ ህግ የሚተዳደር እስላማዊ መንግስት መመስረት የሚል አላማ በመስቀመጥ፣ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ከአልቃኢዳ አልሸባብ የሽብር ተልዕኮ በመቀበል፣ ለዚሁ በመደራጀት፣ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ አባላትን በመመልመል፣ በማደራጀትና ተከታታይ የጦር መሣሪያ አጠቃቀምና አጠቃላይ የሽብር ስልጠና በመውሰድ ሲሳተፉ ቆይተው፤ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሶማሊያ በመሄድ ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ ቆይተው፤ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ፣ አባላትን በማደራጀትና በመመልመል መቆየታቸውን ያስረዳል፡፡
በተከሳሾቹ ላይ ከቀረቡት ምስክሮች በተጨማሪ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች እና በኤግዚቢት የተያዙ ማስረጃዎች ተጠቅሶባቸዋል፡፡
ቀደም ሲል በእነዚህ ተከሣሾች ዙሪያ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት “ጅሃዳዊ ሃረካት” የሚል ዶክመንተሪ ፊልም መተላለፉ ይታወሳል፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 02 November 2013 11:19

‘ቀይ ሽንኩርት…’

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…መቼም የእኛ የብሶት ብዛት ቦታ ላይ እንደሚቆም የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው። የምር…አንዳንዴ እኮ እንደው “ይቺ አገር የምር ባለቤት የላትም…” የምንለው ወደን አይደለም፡፡ አሁንም ብዙ ነገሮችን እያየን እንላለን… “ይቺ አገር ባለቤት የላትም እንዴ?” እንላለን፡፡
“እዚህ ቦታ የጎደለ ነገር አለ ይስከተካከል…” “እዛ ቦታ የተበላሸ ነገር አለና ይጠገን…” ምናምን ሲባል ለምን መደማመጥ እንዳቃተን አይገርማችሁም? ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…እኛ የሚሰማን አለ ብለን ስንናገር አቤቱታ የሚቀርብባቸው ባለስልጣኖች ወይም ሌሎች ግለሰቦች ፌስቡካቸውን ከፍተው (ቂ…ቂ…ቂ…) “ተወው እባክህ ካልደከመው ይለፍልፍ፣ ሀበሻ እንደሆነ ዘላላሙን እንዳለቃቀሰ ነው…” ምናምን የሚባባሉ ይመስለኛል፡፡
ለምሳሌ ስፖርት ላይ ‘ዋይኔ ሩኒ’ የሚባል ሰው እንደሌለና በዛ ስም እየጠራነው ያለው ተጫዋች ትክክለኛ ስሙ ‘ዌይን ሩኒ’ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡ ተጥደን ከምንውልበት የዲ.ኤስ.ቲቪ የሱፐር ስፖርት ዘጋቢዎች በሏቸው፣ በሉት የጀዚራ ስፖርት ዘጋቢዎች በሏችው፣ በየጊዜው ማመሳከሪያነት የምንጠቀምባቸው ‘የህትመት ውጤቶች’ ዘጋቢዎች በሏቸው … አለ አይደል… ከእኛ በስተቀር እንዲህ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ የተጫዋቹን ስም ለውጦ “ባርም አያርመኝ” የሚል ያለ አይመስለኝም፡፡ እናማ… እሺ ቀሸምንና ተሳሳትን እንበል…ማስተካካል ያቃተን ለምንድነው?
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን በስፖርት ዘገባዎች በአተረጓጎም ስህተትም ይሁን በሚገባ ባለማየት ብዙ ስህተቶች ይሠራሉ፡፡ በኢንተርኔትና በ‘ዲሽ’ ዘመን ብዙ ታዛቢ እንዳለ ልብ ይባልማ! ሴትዮዋ ምን አለች አሉ…“አንድ ሰው አንዴ ካታለለኝ ማፈር ያለበት እሱ ነው፡፡ ሁለቴ ካታለለኝ ግን ማፈር ያለብኝ እኔ ነኝ፡፡” እናማ… ዘንድሮ በመረጃ ሰሞን ሁለቴ ተታለው ራሳቸው የሚያፍሩ ሰዎች ቁጥር እያነሰ መሆኑን ማወቀ አሪፍ ነው፡፡
ከተማዋ እየተገለባባጠች ነው፡፡ (“ፈርሳ እየተሠራች ያለች…” የሚለውን ሙሉ ለሙሉ ለመቀበል “ካልታዘልኩ አላምንም…” እንዳለችው ሙሽራ ጊዜ እየጠበቅን እንደሆነ ልብ ይባልልንማ!) ብዙ ቦታ እግረኞች እንደ ልብ መንቀሳቀስ አቅቷቸዋል፡፡ እናማ… ቀጠነችም፣ ጠበበችም መተላለፊያዎች ይሠሩልን እየተባለ ለምን “በእጄ!” ብሎ የሚያዳምጥ እንደጠፋ አይገርማችሁም! አሀ…‘በአፍሪካ መዲናዋ’ ገደሉን ስንወጣና ስንውርድ እኮ ልክ የናሽናል ጆግራፊን ዘጋቢ ፊልም የምንሠራ እያስመሰለብን ነው፡፡
ስሙኝማ…ከእኛው ከጋዜጠኞቹ ሳንወጣ…በኤፍ ኤሞች ላይ ከሚለቀቁ የውጪ ዘፈኖች መካካል ቅልጥ ያለ ‘ብልግና’ (ፖርኖ) ያለበት ብዙ ናችው፡፡ በየጊዜው “ይህንን ነገር ኧረ እባካችሁ…” ይባላል፡፡ ግን ምን መሰላችሁ…አሁንም የለየላቸው ‘የብልግና’ ግጥሞች (አዎ፣ ‘ብልግና’ የሚለው ቃል አሁንም ከመዝገበ ቃላታችን አልጠፋም፡፡) ያላቸው ዘፈኖች እየሰማን ነው፡፡ እና…በኢንተርኔት ዘመን ያልተለመዱ ቃላትን በቀላሉ ማወቅ በሚቻልበት ምነው የምንሰማ ጠፋን!
(ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… የሆኑ ወጣት እንትናዬዎች ደረት ላይ ‘የፈረንጅ አፍ’ ጽሁፍ የተጻፈባቸው ‘ቲ—ሸርቶች’ ለብሰዋል፡፡ እናላችሁ… የጽሁፉ ትርጉም በጣም፣ እጅግ በጣም የሚዘገንን ነው፡፡ እንትናዬዎቹ እንደማያውቁት እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቢያውቁ ኖሮ እንዴት ሊሳቀቁ እንደሚችሉ ይታየኛል፡፡ አሀ…ጽሁፉ ገና ለገና ብሎው (Blow) የሚለው ቃል ስላለበት ከፊኛ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው ማለት አይደለማ!
ስሙኝማ…የዘንድሮ የሙዚቃ ‘ክሊፕ’ መቼስ እንደምታዩት ነው፡፡ መኮረጅ ምን ያህል እንደለመደብን ያሳያል፡፡ ‘ኦርጂናል’ የምትሉት ‘ክሊፕ’ በጣም አናሳ ነው፡፡ እናላችሁ…ቅልጥ ያለ የትከሻ እንቅጥቅጥ ባህላዊ ዘፈን ‘ክሊፕ’ ላይ…አለ አይደል…ከዓለም ሽክርክሪት አሥር እጥፍ በሆነ ፍጥነት ‘ነገርዬውን’ ማሽከርከርን “ኧረ እባካችሁ!” ሲባል ምነዋ ሰሚ ጠፋ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ አዲስ የትራፊክ መብራት እኮ ምን ያህል “ሁሉም ነገር ለእኔ ብቻ…” ባዮች እንደሆንን የሚያሳይ ነው፡፡ መብራቱ ‘ቁም’ ከማለቱ፣ ‘እለፍ’ ከማለቱ ቀደም ሲል ያለችው የማስጠንቀቂያ ብልጭ፣ ድርግም ‘ለመንቀሳቀስ ተዘጋጅ’ ማለት ይመስለኛል፡፡ ግንላችሁ…በዚች ሦስትና አራት ሰከንድ መቆም ያለበትም፣ ለመንቀሳቀስ መዘጋጀት ያለበትም ፈጥኖ ለማለፍ እየተሽቀዳደመ…አለ አይደል… “ዘመናዊነታችን የሪሀናን ዘፈን ከመስማት ሳያልፍ “ሌላኛው ሚሌኒየም ሊመጣ ነው!” ያሰኛል፡፡
አንዳንድ ‘ቦሶቻችን’ ይኸው እስከ አሁን ድረስ ልክ ልካችንን እየነገሩን ነው፡፡ ልትሰሙት ይገባል የሚሉትን ፈቀድንም አልፈቀድንም መንገራቸው አይቀርም፡፡ ግን ቢያንስ፣ ቢያንስ ቃላቶቹን ለምን አይመርጡም፡፡ እዚሀ አገር ሰዉ ወንበር ሲሰጠው አብሮ የማስፈራራት ‘ግሪን ካርድ’ ይሰጠዋል እንዴ! አንዳንዴ ሳስበው…ድሮ ‘ስዩመ እግዚአብሔር’ ይሉ የነበሩት ንጉሣውያን ናቸው፡፡ ዘንድሮ ከኮሚቴ ሰብሳቢ ጀምሮ ያለው ሁሉ ‘ስዩመ እግዚአብሔር’ ነኝ ያዐ ነው የሚመስለው፡፡ እናማ…“ቦታው ላይ የተቀመጣችሁት ልታስተዳድሩን እንጂ እንደፈለጋችሁ ከፍ ዝቅ የምታደርጉን የግል ንብረቶቻቸሁ አይደለንም” ስንል ምነው የሚሰማን ጠፋ፡፡
(ስሙኝማ…እዚህ አገር እንደፈለጋቸው የስሙኒ ኳስ ሲያደርጉን የሚቆዩ ሰዎች ሁሉ በአንድ ወይም በሆነ ምክንያት የሆነ ፌርማታ ላይ “አታስፈልግም” ተብለው ሲጣሉ ለመብታችን ሲከራከሩልን እንደከረሙ ሲያስመስሉ ልክ ግን…አለ አይደል… “እዚህ አገር ክፉ መሆን ብቻ ነው የሚያተርፈው?” ያሰኛል፡፡ ዘንድሮ ነው የምር ጅቦች በማያውቋቸው ሀገራት “ቁርበት አንጥፉልን…” እያሉ ያሉት፡፡)
ዘንድሮ እንደሁ መተማመን አገር ትቶ ተሰዷል። እናማ ምስጢር ምንቋጠር የሚችሉ ሰዎች ኢነዴነጀርድ ስፒሺየስ እየሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የሰማሁትን መቼ ባወራሁት ብለን የምንቁነጠነጥ ሆነናል፡፡ የኃይማኖት አባቶች፣ የማህበረሰብ ጠበብት…ስለመተማመን ሁሌም እያወሩ ነው — ሰሚ ጆሮ ጠፋ እንጂ፡፡
እናላችሁ…ድሮ የአርበኞችን ምስጠር እየሰለሉ ለጣሊያን ሹክ የሚሉ ‘እንቁላል ሻጮች’ ነበሩ አሉ። በዚህ ዘመንም…አለ አይደል… ‘አርአያነታቸውን’ የተረከብን ቁጥራችን የበዛ ይመስላል፡፡ “ስማ…እባክህ ከባለቤቴ ጋር ችግር ገጥሞናል…” ብለን የምናዋየው ሁነኛ ወዳጅ ያጣንበት ዘመን መድረሳችን የምርም የሚያሳዝን ነው፡፡ ምነዋ ምክር አልሰማ አልን!
እንግዲህ ነገሬን ከከንፈሬ አልለቅም
የሰው ዶሮ አለና ከአፍ፣ ከአፍ የሚለቅም
የምትለዋ ነገር ለዘንድሮ ‘በልክ’ የተሠራች ትመስላለች፡፡
ስሙኝማ… አሁን፣ አሁን ከተማ ውስጥ የአሥራ ሁለትና የአሥራ ሦስት ዓመት ህጻናት በጠራራ ጸሀይ ሰክረው ሲንገዳገዱ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ልክ በቲቪ የማይተላለፍ የህጻናት ጣጤዎች ‘ሪያሊቲ ሾው’ ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡ የመጠጥ ማስታወቂያዎች ሁሉ ‘ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የተከለከለ’ የሚል ነገር አላቸው፡፡ ማለትም የመጠጥ ነጋዴዎች “እባካችሁ ለህጻናትና ታዳጊዎች አልኮል አትሽጡ…” እየተባለ ነው፡፡ እናማ… ምነው ሰሚ ጠፋ! ምነው ነገረ ሥራችን ሁሉ “እኔ ከሞትኩ…” አይነት ሆነ! አይደለም ስለሚጠጡ ህጻናት ማሰብ፣ መጠጥን በተመለከተ አዋቂዎችም የሚመከሩበት ዘመን ነበር፡፡
በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ
መጠን አትለፉ ትቃጠላላችሁ
ተብሏል፡፡ ይህንን ስንኝ የጻፉ ሰዎች የዘንድሮ ነገረ ሥራችንን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን! ስንቱ ያለ የሌለውን በመጠጥ እያሟጠጠ አይደል!
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የወጪን ነገር በተመለከተ ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሰውየው ወጪ…ወጪ…ወጪ… ብቻ ሲሆንበት ምን አለ መሰላችሁ…“የእኔ የገንዘብ ቦርሳ እንደ ቀይ ሽንኩርት ነው፣ በከፈተኩት ቁጥር ያስለቅሰኛል፡፡”
እናማ…የሚነገር በዝቶ የሚሰማ ሲጠፋ ነገሩ ሁሉ ‘ቀይ ሽንኩርት’ እየሆነብን ነው፡፡
(‘የሚያስለቅስ የገንዘብ ቦርሳ’ን በተመለከተ…አለ አይደል… እስቲ ለቦርሳ የሚበቃ ፈረንካ ይኑረንና እናየዋለን፡፡”)
ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

Published in ባህል
Saturday, 02 November 2013 11:14

የአዳማ ጉዞ ማስታወሻ!

የደብረ ብርሃን ጉዞዬ ማስታወሻ
ጉዞውን የጀመርነው የ60ዎቹ ወዳጅ ከሆነ ከላፍቶ ከሚመጣው የእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት አማካሪ፤ ጋር ነው፡፡ እኔን ከቄራ ይዘውኝ ወደ ሲ ኤም ሲ እናመራለን፡፡ ከዚያ የዱሮው የዕድገት በሕብረት ወዳጄን እናገኝና ከሱ ጋር ወደ ደብረብርሃን እንቀጥላለን፡፡ ደብረ ብርሃን ስንደርስ የዱሮ ት/ቤቴ፣ የናዝሬት አፃ ገላውዴዎስ፤ ዩኒት ሊደሬ (Unit Leader)ና የዛሬውን የእየሩሣሌም የህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አገኘን፡፡ ግጥምጥሞሹ ይገርማል፡፡ ለረዥም ጊዜ ስላለመተያየታችንና ስለኑሮ ውጣ-ውረድ ከተወያየን በኋላ ወደሥራችን አተኮርን፡፡
መሥሪያ ቤቱ እንዴት ሊቋቋም እንደቻለ እያስረዳኝ ነው ወደ ቀበሌዎቹ መንገድ የጀመርነው፡፡
“ጄክዶ” አለ፡፡ አቶ ዓለማየሁ፤ “ያኔ የነበረውን ችግር ለመቋቋም የተፈጠረ፣ ህፃናቱ ሲያድጉ ምን ይሁኑ በሚል ዓላማ ላይ የተመሠረተ የመጀመሪያ የእሳት አደጋ ሥራ የሠራ ድርጅት ነው!! ነብስ ማዳን!! ቀውሱ እንግዲህ ሲነግሩን በጣም ከፍተኛ ቀውስ ነበረ ነው እሚባለው፡፡ ሞቱ ከፍተኛ ነበር! መታረዙ… መራቆቱ… በሽታው… በየቀኑ ሞት ነበረ ነው እሚባለው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ወደ 500ሺ ሰው ሰፍሮ ነበረ አሉ (ላዕከ አምደሚካኤልን ታቀዋለህ እሱ የኢሠፓ አንደኛ ፀሐፊ ነበረ) ትልቅ ሚና ይጫወት የነበረው እሱ ነበረ… ጋሽ ሙሉጌታ ሀጐስንስ ታቃለህ፤ እሱ እዚህ ዋና ሃላፊ ነበረ፡፡ ሙሉጌታ ሀጐሥ የእኔ አስተማሪዬ ነው - ኤሌሜንታሪ፡፡ ህያው ዋጋ ነው።
አቅመ ደካማ የሆኑና እናት አባት የሌላቸው፤ ሲቀሩ፤ ማን እነዚህን ይታደግ ብለው ሲጠይቁ ጄክዶ ተወለደ፡፡ በጊዜ ሂደት 250 ልጆች ተወለዱ፡፡ ሲያሳድጉ ቆዩ፡፡ እዚሁ ግቢ ውስጥ መምህር ይቀጠርና ይማሩ የሚል ሃሳብ መጣ!”
ታሪኩ ዱሮ፤ እንዲህ ነው፡፡ አሁን ቢሮው ያለበት ግቢ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ አርፎ ነበረ - ለመጠለያ፡፡ ከዛ ውስጥ በተወሰነ እርሾ ተጀመረ - ህፃናትን መርዳት፡፡ ማን ይታደጋቸው ሲባል ነው ጆክዶ (የእየሩሳሌም የህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት) የተወለደው፡፡ ያን ጊዜ ስሙ ጂሲኤች) ጂሩሳሌም ቺልድረንስ ሆም ነው የመጀመሪያው፡፡ እየሩሳሌም የህፃናት ማሳደጊያ፡፡ የደብረብርሃን የህፃናት ማሳደጊያ፣ የባህር ዳር፣ ያዲሳባ፣ የመንደፈራ ማሳደጊያ ነው በየቦታው ስሙ፡፡ የመጀመሪያው አዲስ ዓለም ነው፡፡ ቀጥሎ ደብረ ብርሃን ነው፡፡ ቀጥሎ ባህር ዳር፡፡ ከዛ መንደፈራ ነው፡፡ በዩኒፊኬሽኑ (መልሶ መቀላቀሉ) ብዙ ልጆች በሪኢንቴግሬሽኑም እንደዚሁ ብዙ ልጆች ነው ከቤተሰብ የተዋሃዱት፡፡ የልጆቹ ቁጥር እያነሰ ሄደ በግቢው ውስጥ ያሉት፡፡ ሲጀመር፤ ውስጥ የነበሩትና ቀጥሎ ደግሞ ከትግራይ፣ ከወሎ፣ ከጐጃም ወዘተ የመጡት ቁጥር ሰፊ ነው፡፡
በብዛት ከትግራይ የመጡ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ወሎ ነው። ከዛ ሰሜን ምሥራቅ ሸዋ አለ፡፡ ጐጃም (በቁጥር ትንሽ)፣ ጅማም (በቁጥር ትንሽ)፡፡
አሁን ቀበሌ 02 ውስጥ ነን (ብሎ መኪናውን አዞረው። “መንግሥት ተቀበሉ ሲለን እምቢ ስንል ቆየንና ተቀበልን፡፡ በኋላ self assessment (ራስን መፈተሽ) ተጀመረ፡፡ በህፃናት ማሳደጊያ ማሳደግ፤ ምንድን ነው ችግሩ? የሚለውን እናይ ነበረ - እኔም ደርሼአለሁ፡፡ ልጆቹ ህብረተሰቡን ይሸሻሉ፡፡ ከውጪ እንኳን ጓደኛ አይዙም፡፡ እዛው ነው በቃ የራሳቸው ደሴት የሚመሠረተው ውጪ አይቀላቀሉም፡፡ ት/ቤትም እንደዚሁ ነበሩ፡፡ በትምህርት ግን በጣም የሚገርሙህ ናቸው፡፡ ለምን? ግማሽ ቀን ነበር የሚማሩት፡፡ ቲቶሪያል አለ፡፡ ግማሹን መምህራን ተቀጥረው ያስተምሯቸዋል፡፡ በቃ መማር ነው ሥራቸው፡፡ ሙሉ ቀን ትምህርት ናቸው፡፡ “የኢየሩሳሌም ልጆች ተማሪዎች” ምርጥ ውጤት ያላቸው ናቸው፤ ነው ሚባሉት፡፡ Reunified አንሆንም ነበረ አቋማቸው ግን! አይፈለግማ!
ቅዳሜ ቅዳሜ ገበያውን እንዲያዩ ማድረግ፣ አትክልት እንዲሸጡ (ገንዘብ ምንዛሪውን እንዲያውቁ) ብዙ እንጥር ነበር። በማ/ሰባዊ ግንኙነት አንፃር ከእናቱ፣ ካክስቱ ጋር የሚኖር ልጅ ይለያል፡፡ እራሱን ትዳብሰዋለች - ፍቅር አለ፡፡ የእኛ አርቲፊሻል ነው፡፡ እዛ ሰብዓዊ ትኩሳት ነው ስለሆነም እንቀላቅላችሁ ስንል የነበረው ግርግር ሌላ ነው፡፡ ከዛ ዞሮ ዞሮ ተቀላቀሉ፡፡ ከመንግሥት ጋር በመሆን በየገበያው ሁሉም የሥራ ባልደረቦች ተረባርበን ሠራን፡፡ ከዛ የራሳችንን ግምገማ ማካሄድ ጀመርን፡፡ ቀድሞም ጥናቱ ነበረን፡፡
በተመልሶ ከቤተሰብ መዋሃድ የልጆቹ ቁጥር እያነሰ እያነሰ ሲሄድ ኮሙኒቲ ውስጥ ገባን፡፡ በመጀመሪያ የገባነው ቀበሌ ዘጠኝ ነው፡፡ ቀጥሎ ቀበሌ 4 ቀጥሎ ወደ 5 ቀበሌዎች ገባን፡፡ እንግዲህ እንሠራ የነበረው ሥራ መጀመሪያ ሁለት ሥራ ነው፡፡ የሠራነው 1ኛ/ ዕውቀቱ ስለነበረን፣ እኛ ቀደም ቀደም አልንና ፕሮጄክት እየሰራን ጀመርን (ቀበሌ 9 ላይ) ማደራጀት ጀመርን፡፡ ጥናታችን ታሪካዊ ነው፡፡
ስንጀምር ከዞን ጀምረን እስከ ወረዳ የሚመለከታቸውን የትምህርት፣ የጤናም፣ የግብርናም፣ የከተማ ትምህርትም ብቻ ሁለት ሁለቱን እያጣመድን አመጣን፡፡ ያ ዘዴ እንዴት እንደጠቀመን ግን ልነግርህ አልችልም፡፡ ራሳቸው ፋሲሊቴተር ሆነው ቁጭ አሉልህ፡፡ እናቶችን ለብቻ፡፡ ወጣቶችን ለብቻ፡፡ አረጋውያንን ለብቻ፡፡ እነሱ አመቻች ሆኑልን፡፡ ወደዛው ፕሮጄክት አደረጉልን ማለት ነው፤ ባለቤት ሆኑልን ማለት ነው፡፡ ታሪካዊ እምልህ ለዚህ ነው፡፡”
“ለምን ከ09 ጀመራችሁ?” አልኩት፡፡
09 ካምፕ ነው፡፡ ስትገባ የመጀመሪያው - ጠባሴ፡፡ አባት የለም (አብዛኛውን አባት የለም family headed ይሆን የነበረው በእናቶች ነው) አባት ወይ ሰሜን ጦርነት ሄዷል፤ ወይ ሞቷል፣ አንዳንዱም ምንም አይታወቅም፡፡ የወታደር ባህሪ ነው ያለው። ከመንግሥት ጋራ በጋራ አጥንተን፣ እያንዳንዱን ቀበሌ ተንትነን አውቀን፣ የመጨረሻው ደሀ አዚህ መሆኑን አየን። በትክክል ከዛ ጀመርን፡፡ የትምክህት ኮሚቴ፤ የጤና ኮሚቴ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት ኮሚቴ፣ አቋቋምን፡፡ ቀስ በቀስ ወደ ማህበረሰብ ይዞታ አሸጋገርን! ኮሚቴዎችን አንድ ላይ አደረግንና የመጀመያውን ማኅበራችንን ያቋቋምነው ቀበሌ 9 ነው፡፡ ይሄንን ልምድ ወደ ሌሎቹ ቀበሌዎች ወሰድን፡፡ አብዛኛዎቹ ከኛ ጋር የሚሠሩት ማህበራት ራሳቸውን ችለዋል፡፡ ቀበሌ 9 የነበረው ዛሬ በሁለት ተከፈለ 09/07፡፡
አሁን የምታየው እንግዲህ አንድ ራሱን ችሎ የቆመ (graduate ያደረገ) ማህበር ነው፡፡ እያንዳንዱ ቀበሌ ላይ የምታየውን አሁን መንግሥት “የልማት በጐ አድራጐት” ብሎታል፡ ምዝገባው (Registration) ላይ አታግሎናል፡፡
ጐጃም ውስጥ የልምድ ልውውጥ ፕርግራም ወሰድን፡፡ እዚያ ሄደው አይተው ሲመጡ፤ በዕውነት ትልቅ ለውጥ ነው ያየነው፡፡ አገዘን፡፡ ሌላጋ አዩት፡፡ የተቀደሙና የቀሩ መሆኑን አዩት፡፡ ለውጥ መጣ!! ከዛ አዲስ ነገሮችን አመጣን - የዕድሮችን ህብረት ማቋቋም ጀመርን፡፡ አንዳንዱ ቀበሌ ላይ የዕድሮች ህብረት አለ Self Help Group፣ Cluster Level Association፣ Federation እና Confederation፡፡”
እንግዲህ ይሄን ይሄን ስናወራ ቀበሌው ጋ ደረስን፡፡ ጋሽ ዓለማየሁ ከአመራሮቹ ጋር አስተዋውቆኝ ሄደ፡፡ እኔ ከማህበሩ ፀሐፊ ከወይዘሪት ኤልሳቤጥ በርሃኑ ጋር ውይይት ቀጠልኩ፡፡
“ቀድሞ ጄክዶ እዚህ ቀበሌ 08 ውስጥ ልማታዊ ሥራዎችን ይሠራ ነበር፡፡ እኔ በጐ ፈቃደኛ ሆኜ ሰርቻለሁ - ሲመሰረት ጀምሮ አለሁኝ፡፡
ይህ ማህበር 96/97 ዓ.ም ከተቋቋመ በኋላ ይሄንን ማህበር የነሱ ሥራ ቀጣይነትና ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ፣ ማ/ሰቡ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማሰባሰብና በማደራጀት እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የማ/ሰብ ክፍሎች ናቸው:: ሲመለመሉ በዕድሮች ነው፡፡ በንዑሳን እድሮች በየቀጠናው ኮሚቴዎች አሉ፡፡ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ ብለን የመጣውን ሰው እንመዘግባለን፡፡ የዕድሮች አመራሮች፣ የቀጠና ንዑሳን ኮሚቴዎች፣ የቀበሌ አመራሮች ባሉበት ቁጭ ብለን እናያለን::
አሁን ግን ቀበሌ ላይ ጥምረትና እንክብካቤ ተቋቁሟል። በዛ መሰረት፤ ችግርተኞች ዞረን አይተን ድጋፍ ይገባቸዋል የምንለውን እናረጋግጣለን:: ወደ ድጋፉ እንገባለን:: 5 ፕሮግራሞች አሉን:- 1ኛ/ ህፃናት ላይ 2ኛ/ ትምህርት ማጠናከሪያ ላይ 3ኛ/ግብርና ላይ 4ኛ/ ጤና ላይና 5ኛ/ ኑሮ ማሻሻያ ላይ፡፡
ማህብረሰቡ /ዝቅተኛ ሁኔታ ላይ ያለው/ ተጠቃሚ እንዲሆን ነው የምንሠራው:: ማህበሩ የሚመራው በቮለንቲር ኮሚቴዎች ነው:: ነፃ አገልግሎት ማለት ነው፡፡ ቢያንስ እኔና እሱ/ ታምራት /እዚህ እምታዩት ሱቅ - የተወሰነ የኪስ ገንዘብ ለጠባቂ ለሻጭ(ማረጋጊያ ሱቅ) እና ለኛ የኪስ ገንዘብ እየተሰጠን ነው እምንሠራው:: ሰባት አባላት ያሉት ንዑስ ኮሚቴ ኦዲትና ቁጥጥር አማካሪ ቦርድ አለን:: ማህበሩ ሲቋቋም ከማህበረሰቡ የተውጣጣ ከሚቴ ነው በበላይነት የሚመራው፡፡
“ገቢያችሁ ምንድን ነው?” አልኳቸው፡፡ ገንዘብ ያዡ አቶ ግርማ መለሱልኝ፡- የእህል መጋዘን አለን፡፡ አንድ ባጃጅ አለችን - በተገኘው ገንዘብ የተገኘች፡፡ ዕድሜ ለጄክዶ (የእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ድርጅት) የተገኙ የወተት ላሞች አሉ። ጽ/ቤት፤ በፊት እየተከራየን ነበር - ከቦታ ቦታ እየሄድን ነበር የምንሠራው፡፡ አሁን ግን ደፈር አልን፡፡ ቦታውን ገዝተን የማኅበሩን ቢሮ እዚህ አደረግን፡፡ ድጋፍ አድራጊዎቹ ፌዝ-አውት አድርገዋል:: እኛ ግን ራሳችንን ችለናል::
የጄክዶን አስተዋጽኦ ስትል ኤልሳቤጥ ፍጽም ፈገግታ አላት፡፡ ታምሩ ኪዳኔ የተባለው የበጐ አድራጐት ሥራ ባልደረባዋ ተቀበላት -
“በዝቅተኛ ዋጋ ለህብረተሰቡ እህል ያቀርባል:: ገበያውን የሚያረጋጋና ህብረተሰቡን ተደራሽ ነው:: ላሞቹ አንድ አመት ግድም ነው ከመጡ:: ይታለቡና ወተት ለሚሰበስቡ ድርጅቶች ይሰጣል:: ባንክ ገቢ ይደረጋል፡፡ የራሳቸው አካውንት አላቸው። ከዛ ለቀለባቸው ይወጣል፡፡ ተዘዋዋሪ ፈንድ ይደረጋል” አለ::
ኤልሣ ቀጠለች “ወተቱ ላካባቢው አገልግሎት ይሰጣል፤ ተረፈ ምርት ነው፡፡
አካባቢው አረቄ አውጪ ስለሆነ ኩበት የመግዛት ዕድል ያገኛል
ቫይረሱ በደማቸው ላለ ህፃናት የትኩስ ወተት ድጋፍ እናደርጋለን
ከቀለብ በተረፈው ንፅህና አልባሳት፣ የጫማ፣ የትምህርት መሳሪያ፤ ድጋፍ እናደርጋለን
ሁለት ሥራ አጥ ወጣት ተንከባካቢና አላቢ በመሆን የሥራ ዕድል አግኝተዋል”፡፡ በረት ጠራጊ + ወተት አመላላሽ + ጥበቃ ሠራተኞችም አሉ::
ዕድሜ ለእየሩሳሌም የህፃናትና የህብረሰብ ልማት ድርጅት!” አለች፡፡
“ወደ ፊትስ ለዘለቄታችሁ ምን አደረጋችሁ?” አልኳት፡፡
“ወደፊት እዛው አካባቢ ላይ ሻይ ቤት ነገር ከፍተን ወተቱን ለነጋዴ ከመስጠት እርጎም፣ አይብም፣ አጓትም እንሸጣለን፡፡ ገቢ ማስገኛ ነው፡፡ ነገ ይገባል ብለን የምናስበው የዳቦ ማሽን ከበጐ አድራጊ አግኝተናል:: ዳቦና ወተት በቅናሽ! ማህበረሰቡ ይጠቀማል፡፡ በተጨማሪ በጉባዔው በዓመት ሁለት ጊዜ ስብሰባ አለን፡፡ ወጣቱንም፣ ሴቱንም፣ ጎልማሳውንም የሚወክለውን እናገኘዋለን:: የሃይማኖት አባቶችንም እናወያያለን፡፡”
“ቀበሌውም አብሮን አለ” አሉ አቶ ግርማ:: አመኔታው ላይ መጀመሪያ ብዥታ ነበር:: ለ3ዓመት ተመርጠን ነው - ሁለተኛ ዙር ላይ ነው ያለነው፡፡ መጀመሪያ ህብረተሰቡ አልገባውም ነበር፡፡ “ከኔ እሚበልጡ ታዋቂ ተደማጭነት ያላቸው አሉ… ለምዝበራ ማይጋለጡ መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቃል:: ሂሳብ አያያዛችን አይጠረጠርም- ዘመናዊ ነው፡፡ ቦርዶች አሉን - መጥተው ይገመግሙታል::
ወደፊት ውጤታማ እንሆናለን! ቮለንተሩ አይደክምም በውጤቱ ደስተኛ ነው! ጥቅምም ባይኖረው በህብረተሰቡ ጥቅም ስለምንረካ ጉልበታችንን መስዋዕት እናደርጋለን:: ከሌላ ቀበሌዎች ጋራ የልምድ ልውውጥ እናደርጋለን:: ጄክዶ ፕሮጄክቱን ጨርሶ ቢወጣ እንዴት ዘላቂ እንደምንሆን ስላሰለጠነን እናውቅበታለን፡፡
ህብረተሰቡ የራሱን ፈጠራ ይሰራል:: ራሱ መንቀሳቀስ ሲችል እንጂ በእርዳታ የትም አይደረስም! ገቢውን ማምጣት፣ ማመረትና ራሱን መቻል አለበት”::
ልበ - ሙሉነታቸው በጣም ደስ አለኝ፡፡
ከሰዓት በኋላ የከተማ ግብርናን መሠረት አድርጐ ወደተመሠረተው የቀበሌ ማህበራት ስብሰባ ልሄድ ተሰናብቻቸው ከጋሼ ዓለማየሁ ጋር ወደምሣዬ ተጓዝኩ፡፡
(ጉዞዬ ይቀጥላል)

Published in ባህል

በታላቁ መጽሃፍ “መጽሃፍ ቅዱስ” ላይ በመጽሃፈ ነገስት ቀዳማዊ ላይ በምዕራፍ 10 ከቁጥር 1 እስከ 13 ድረስ ንግስተ ሳባ ጠቢቡ ሰለሞንን ጎብኝታ ወደ ሃገሯ እንደተመለሰች ይናገራል፡፡ ዓረቦች ይህንን ታሪክ የግላቸው ለማድረግ መጠነ ሰፊ ጥረት አድርገዋል፤ ባይሳካላቸውም፡፡ ንግስተ ሳባ የራሳቸው ንግስት በመሆን ጠቢቡን ጎብኝታ ለመመለሷ እንደ ማስረጃ የሚያነሱት በዓረቦች ውስጥ የሳባ ዓረቦች የሚባሉ ነገዶች ነበሩና የነሱም መጠሪያ ይህችው ሳባ ናት በማለት ነው፤ የርሷም መነሻ ዓረብ ነው በማለት፡፡ “ንግስተ ሳባ የኛ የሃገራችን ንግስት ሆና ጠቢቡ ሰለሞንን ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም ከኢትዮጵያ ሳይሆን ከሃገራችን ተነስታ ሄደች፡፡” የሚልም በመጽሃፋቸው “በቁርዓን ሲራ 27” ላይ ሰፍሯል፡፡ የኛ ኢትዮጵያኖች ደግሞ “አይደለም ተሳስታችኋል… ንግስተ ሳባ ኢትዮጵያዊት ነች እንጂ እናንተ እንደምትሉት ዓረብ አይደለችም፡፡” በማለት ቀደምት አባቶቻችን ሞግተዋል፡፡ እኔም ከዚህ በኋላ በየደረጃው ኢትዮጵያዊት መሆኗን የሚያስረዱ ምክንያቶችን እያነሳሁ አልፋለሁ፡፡
ከቀደምት አባቶቻችን ከወረስናቸው የታሪክ መጽሃፍት እንደምንረዳው@ ንግስተ ሳባ ኢትዮጵያዊት ንግስት ብሎም የቀዳማዊ ምኒልክ እናት መሆኗን አረጋግጠናል፤ በዘመኗ ከመንግስቷ ኃያልነት የተነሳ የግዛቷ ስፋት የዓረብ ሃገራትን ያካትት ነበር፡፡ በመሆኑም እርሷ ጠቢቡን ለመጎብኘት ግዛቷ በሆኑ የዓረብ ሃገራት በኩል ለንጉሱ የሚሆን እጅ መንሻና አምኃ በግመሎቿ አስጭና እንደሄደች የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ዓረብ ሳትሆን ኢትዮጵያዊት ንግስት ነች፡፡
በመጽሃፍ ቅዱስ የንግስተ ሳባ@ ንጉስ ሰለሞንን መጎብኘቷን ከመተረኩ በተጨማሪ በሌሎች ኢትዮጵያዊ መጽሃፍት ላይ ንግስተ ሳባ “ማክዳ” (በጊዜው የንግስት ሳባ መንግስት መቀመጫውን ያደረገባት የኢትዮጵያ ከተማ ነች) እየተባለች ተጽፋለች፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙት ታላላቅ መጽሃፍት መካከል አንዱ “ክብረ ነገስት” ነው፡፡ በዚህ መጽሃፍ ላይ የኢትዮጵያ ንግስና በቀጥታ ከንጉስ ሰለሞንና ከንግስት ሳባ ልጅ በሆነው በቀዳማዊ ምኒልክ እንደወረደ እንዲህ ይተርካል “ከጌታ ልደት በኋላ በ325ዓም በኒቅያ ጉባዬ ለተሰበሰቡት ሮማዊው ፓትሪያርክ ዶሚስዩስ@ ከቅድስት ሶፍያን ቤተክርስቲያን ውስጥ ባለው መጽሃፍ ላይ “የኢትዮጵያ ንጉስ በቀጥታ (በብኩርና) መስመርና ተርታ ከሰለሞን ንጉስ ይወርዳል፤ የሮም ንጉስ ግን በታናሽነት መስመር ይወርዳል፡፡” የሚል አለ ይሄው መጽሃፍ ደግሞ የኢየሩሳሌንምን ግማሽና የዓለምን ደቡብ በሙሉ ለኢትዮጵያ ንጉስ’ የቀረውን የኢየሩሳሌምን ክፍልና የሰሜንን ክፍል ለሮም ንጉስ ይሰጣል ብሎ ለጉባዬው ነገራቸው፡፡” የሚል እናነባለን፡፡
ይህ በአስረጅነት ያቀረብነው መጽሃፍ እንደሚለው’ንጉስ ሰለሞንን ለመጎብኘት የሄደችው ኢትዮጵያዊቷ ንግስት ማክዳ ናት፡፡ የሳባ ነጋዴዎች በባህር እስከ ህንድ፣ በየብስም እስከ ሴኤን (አስዋን የግብጹ) ድረስ እየሄዱ ትልቅ ንግድ ይነግዱ ነበር፡፡ ከነዚህ ነጋዴዎች አንዱ “ታምሪን” የተባለው ነጋዴ ስለ ንጉስ ሰለሞን እጅግ በጣም የሚያስገርም ነገር ነገራት፤ ይህን በሰማች ጊዜ ንጉስ ሰለሞንን ሄዳ ለመጎብኘት ተመኝታ ለንጉስ የሚገባ እጅ መንሻና አምኃ የሚሆን በብዙ ግመል አስጭና ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ንጉሱን ካየች በኋላ ወደ አገሯ ተመለሰች፡፡ ዳሩ ግን አገርዋ ሳትገባ “በላ-ዘዲዛርያ” አጠገብ አንድ ልጅ ወለደች፡፡ ልጁም “በይነ ለሐኪም” (የሳባ ልጅ በክብረ ነገስት ላይ “በን ለሐኪም” ብሎ ይጠራዋል፡፡ በን ለሐኪምን በይብራይስጡ “በን ሀሐካም”፣ ዓረቦቹ “ኢብን ኤል ሐኪም” የተባለው ፍቺው “የጠቢብ ልጅ” የሚል ነው፡፡ በግዕዙ “መኑ ይልህቅ” በመጨረሻም “ምኒልክ” ብሎ ይፈታዋል።) በይነ ለሐኪም 22 ዓመት ሲሞላው የንጉሱን ጥበብ ለንግስቲቱ ከነገራት ነጋዴ ታምሪን ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፡፡ የሄደበትም ምክንያት ንጉስ ሰለሞን ለኢትዮጵያ ንጉስነት እንዲቀባውና ሃገሪቱንም ከአረመኔነት (ከአረማዊነት) ለማውጣት በማሰብ ነበር፤ አካሄዱም ከንግስት ሳባ የተላከ መልዕክተኛ ሆኖ ነበር፡፡ ንጉስ ሰለሞን ግን የመልኩን መምሰልና ለንግስቲቱ ማስታወሻ ብሎ የሰጣትን ቀለበት በማየት ልጁ እንደሆነ ካረጋገጠ በኋላ’ “ሮብዓም” የተባለው ልጁ ገና የስድስት ዓመት ልጅ ስለነበረ’በን ለሐኪምን በእስራኤል መንግስት ላይ ወራሹ እንዲሆን ፈልጎ ነበር፤ በን ለሐኪም ግን ፈቃደኛ አልነበረም፡፡
የበን ለሐኪምን ፈቃደኛ አለመሆን የተቀበለው ንጉስ ሰለሞን ‘ልጁን ከሸዋ ደቡብ እስከ ህንድ ምስራቅ ድረስ በተዘረጋው ምድር ላይ የኢትዮጵያ ንጉስ አድርጎ በጊዜው በነበረው ካህን “ሳዶቅ” አስቀባው፡፡ ንጉሱም በኢየሩሳሌም የሚሰሩትን ታላላቅ ስራዎች በኢትዮጵያ ከበን ለሐኪም ጋር እንዲፈጽሙ በማሰብ’ ከእስራኤል ትልልቅ ሰዎች የተወለዱትን ጨምሮ ላከው፤ እነሱም ከኢየሩሳሌም ሲነሱ ጽላተ ሙሴን ከቤተ መቅደስ አውጥተው ወሰዷት፡፡ ታቦተ ጽዮን መወሰዷን የሰማው ንጉስ ሰለሞን@ልጁ በን ለሐኪምን ተከታትሎ ሊመልሳት ፈልጎ በጣም በመራራቃቸው የተነሳ ሊደርስባቸው ባለመቻሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡ በን ለሐኪምና ተከታዮቹ በሰላም ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ገቡ፡፡ ወደ ግዛታቸው ከገቡም በኋላ በአዜብ፣ በዋቂሮና በሜዛስ አልፈው ከከተማቸው ደብረ ማክዳ ደረሱ፡፡ ጽላተ ኪዳኗንም ከተራራ አናት ላይ አኖሯት፡፡ በይነ ለሃኪምም የመንግስቱን ስልጣን ከንግስት እናቱ ሳባ ተረከበ፡፡ ሌዋውያንና ሌሎቹ ከኢየሩሳሌም የመጡት ነገዶች ሁሉ በመንግስቱ ግዛት ላይ ሃይማኖትንና የብሉይ ሥርዓትን (የእስራኤል ትዕዛዛት) አቆሙ፡፡ መንግስቱም በሃይልና በብስለት የተጠናከረ ሆነ፡፡
በ1940ዎቹ በኣባ ፓስፓራኒ (በጊዜው የአስመራ ኮምቦኒ ኮሌጅ ዳይረክተር ነበሩ) “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል መጽሃፍ ላይ የመንግስቱን ሃያልነት ሲናገሩ “በን ለሐኪም መንግስቱን ካደላደለ ከጥቂት ወሮች በኋላ ዘመቻ አደረገ፡፡ ሰፈሩንም “ከማየ አበው፣ የአባቶች ውሃ” (በዓባይ ዙሪያ ላይ ያለ ቦታ እንደሆነ ይገመታል) ላይ አደረገ፡፡ ከዚያ የዞውንና የሃዲያን መሬት ያዘ፤ ከዚያ ቀጥሎ ኖባንና ሶባን ወግቶ እስከ ግብጽ ወሰን ድረስ ዘመተ፡፡ የግብጽና የምድያም ነገስታት በጣም ፈርተው ሰላማዊነታቸውን የሚያስታውቅ መተያያ ላኩለት፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሃገሩ ተመልሶ ከከተማው ገብቶ እንደገና ወደ ህንድ ቢዘምት ንጉሱ እጅ መንሻ አቅርቦለታል፡፡” በማለት የቀዳማዊ ንጉስ ምኒልክ መንግስት ምን ያህል ኃያል እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
የንግስተ ሳባ ጠቢቡ ሰለሞንን መጎብኘት እጥፍ ድርብ የሆኑ አላማዎችን ያካተተ ነበር፤ ንግስተ ሳባ የሄደችበት ዓላማ በራሱ እርሷ የኢትዮጵያ ንግስት እንደነበረች ያመለክታል፡፡ አንድ ሁለቱን እንመልከት:-
የመጀመሪያው ዓላማ ተብሎ የሚወሰደው በእንቆቅልህና በምሳሌ የሰለሞንን ጥበብ ለመርመርና ለመፈተን መጓዟ ነው፤ ንጉሱ ጥበብ አዋቂ በመሆኑ መደነቋም የግብጽና የባቢሎን ነገስታት አስቸጋሪ ጥያቄዎችን (እንቆቅልሾችን) ምሳሌ እየቀረቡ ከሊቃውንት ጋር መነጋገር መውደዳቸውን በታሪክ እናገኛለን፤ ኢትዮጵያም የዚህ አካል ነበረች፡፡
ሌላኛው የንግስተ ሳባ ዓላማ በእርሷና በሰለሞን መንግስት መካከል የንግድ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ መፈለጓ ነበር፡፡ እርሷ በሃገሯ የሞላውን ሽቱ፣ ወርቅ፣ ዝባድና የተከበሩ ድንጋዮችን (የነዚህ ማዕድናት መገኛ ኢትዮጵያ መሆኗን ልብ ይሏል) በመላክ በሃገሯ የማይገኙትን የንግድ እቃዎች መውሰድ በመፈለጓ ነው፡፡
ለዚህ ጽሁፍ የመጨረሻ የማደርገውና በርግጥ ንግስት ሳባ ኢትዮጵያዊ መሆኗን ማስረዳት የሚችለው የንጉስ ሰለሞንና የንግስት ሳባ የንግስና ዘመናቸው አንድ መሆኑ ነው፡፡ በክብረ ነገስት ላይ እንደሚገኘው ታሪክ@ ንጉስ ሰለሞን ከጌታችን ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በ1972 እስከ 1932 ዓዓ ድረስ በኢየሩሳሌም ላይ ልክ ለ አርባ ዓመታት መንገሱን ይነግረናል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ንግስተ ሳባ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የነገስታትን ተርታና ትውልድ ያየን እንደሆነ’ ሳባ ከጌታችን ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት ከ1982 እስከ 1957 ዓዓ ድረስ በኢትዮጵያ ላይ ለሃያ አምስት ዓመታት እንደነገሰች የሚያመለክት የታሪክ ጽሁፍ እናገኛለን፡፡ በመሆኑም ጠቢቡ ንጉስ ሰለሞንና ኢትዮጵያዊቷ ንግስት ሳባ የነገሱባቸውን አዝማናት ያየን እንደሆነ ያለ ጥርጥር ይህች ንግስት ኢትዮጵያዊት ነች ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ነገስታት ታሪክ ላይ የሚገኘው ቀዳማዊ ምኒልክም የስሙ ትርጓሜ “የጠቢብ ልጅ” ተብሏልና ይህም ጠቢብ ታላቁ የኢየሩሳሌም ንጉስ ጠቢብ ሰለሞን ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ