የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ሰዓሊዎች ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት የስዕል አውደርዕይ ነገ ከጠዋቱ በ4 ሰዓት በፓሽን በርገር ይከፈታል፡፡
ሬንቦ ጋለሪ ባዘጋጀው በዚሁ የስዕል አውደርዕይ ላይ የአካል ጉዳተኝነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም እንደሚኖር ለማወቅ ተችሏል፡፡ አውደርዕዩ እስከ ማክሰኞ ድረስ ለሶስት ቀናት ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

Monday, 25 November 2013 11:09

“ሮዛ” ለንባብ በቃ

በአሁኑ ሰዓት ኑሮዋን በዱባይ ባደረገችው ሮዛ ይድነቃቸው የተዘጋጀው “ሮዛ” የተሰኘ መፅሃፍ ታትሞ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ አዘጋጇ ቀደም ሲል ባሳለፈችው የቡና ቤት ህይወት ውስጥ የከተበቻቸውን የዕለት ማስታወሻዎች አሰባስባ ነው መፅሃፉን ያሳተመችው፡፡ 223 ገፆች እና 29 ታሪኮችን ያካተተው ይሄው መፅሃፍ፤ በሊትማን መጽሀፍት መደብር በ49 ብር ለአንባቢያን ቀርቧል።

ባለፈው ሳምንት “ንግሥ” በሚል ርዕስ የተከፈተው የመዝገቡ ተሰማ የስዕል ኤግዚቢሽን ከበርካታ ተመልካቾች እና ሰዓሊያን አድናቆትንና ምስጋናን ያተረፈ ሲሆን፣ በሚቀጥለው አርብ ውይይት ይካሄድበታል ተብሏል፡፡ በ“ሮማንቲክ ሪያሊዝም” ዘይቤ ትላልቅ ስዕሎችን በመስራት የሚታወቀው መዝገቡ ተሰማ፣ 5 ሜትር በ2 ሜትር ስፋት ያለው “ንግሥ” የተሰኘ ስዕልን ጨምሮ 15 አዳዲስ ስዕሎችን ለእይታ አቅርቧል፡፡ በቀለም አዋቂነቱ፣ በምስል ቅንብር ጥበበኛነቱ እና በምጡቅ ክህሎቱ የሚደነቀው መዝገቡ ተሰማ፤ የስዕልን የ “3D” ባህርይ አጉልቶ ለማውጣት አዳዲስ ስልቶችን ተጠቅሟል፡፡
በስዕሎቹ ላይ በሚቀጥለው አርብ በ8 ሰዓት ውይይት የሚካሄደው፤ እዚያው የስዕል አውደ ርዕይ በሚታይበት ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ነው፡፡ መዝገቡ ተሰማ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነጥበብ አስተማሪ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  

                ሀገራችን ኢትዮጵያ የረዥም ዘመናት ታሪክ ባለቤት ብትሆንም ሐብትንና ዕውቀትን አቀናጅቶ፣ በጋራ ሰርቶአብሮ በማደግ ረገድ ግን ብዙ ይቀረናል፡፡  ለዚህም ይመስላል “ኢትዮጵያዊያን አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አይሆንላቸውም” የሚባለው፡፡
ዛሬም በ21ኛው ክ/ዘመን እንኳን በሀገራችን በአክስዮን ማኅበራት በመሰባሰብ መሥራት  በተግዳሮቶች የተሞላ ሆኗል፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የተቋማት ተገቢው ዕውቀት ባላቸው አካላት አለመመራት ይመስለኛል፡፡ አልፋ የትምህርትና ስልጠና አክሲዮን ማኅበር ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ትምህርትና ሥልጠና ታሪክ ውስጥ የተለየ ቦታ ያለው አልፋ የትምህርትና ሥልጠና አክስዮን ማኅበር፤ መሠረቱ “ብሔራዊ ሙያ-ነክ የተልዕኮ ትምህርት ድርጅት” የተባለው በአንድ ግለሰብ ንብረትነት በ1974 ዓ.ም የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ተቋሙ የተመሠረተበት ዓላማ፣ የዳበረ ልምድ እያላቸው የቀለም ትምህርታቸውን ያላሻሻሉ በርካታ ዜጐች፤ የንድፈ ሃሣብ እውቀታቸውንና የሙያ ክህሎታቸውን በርቀት ትምህርት አሳድገው ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ለማስቻል ነበር፡፡
ይህ ተቋም በ1986 ዓ.ም ከግል ንብረትነት ወደ ብዙሃን ሐብትነት ተሸጋገረ፡፡ ስሙም “አልፋ የትምህርትና ስልጠና አክስዮን ማህበር ተሰኘ፡፡ ኩባንያው በ32 መሥራች አባላት የተቋቋመ ሲሆን እነዚህ አባላት መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎችና የንግድ ማኅበረሰቡን ያካትታሉ፡፡ የዚህ ስብስብ አባላት ዓላማ በሀገራችን የትምህርትና ሥልጠና ሥራ በስፋትና በጥራት እንዲከናወን ተገቢውን የሙያ አስተዋጽኦ ለማድረግና በሂደቱም በሚገኝ ትርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ነበር፡፡
ዛሬ ላይ ሆነን ስናሰላው “ብሔራዊ ሙያ ነክ የተልዕኮ ትምህርት ድርጅት” ከተመሠረተ 32 ዓመታት፣ “አልፋ የትምህርትና ሥልጠና አክሲዮን ማህበር” ከተመሠረተ ደግሞ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኩባንያው በ1990ዎቹ መጨረሻ ዓመታት “የት ሊደርስ ነው” እንዳልተባለ ሁሉ በአሁኑ ወቅት ያለበት ደረጃ ግን በእጅጉ አሳዛኝና አሳሳቢ መሆኑ የማህበሩ አባላት ሁሉ የሚያውቁት እውነት ነው፡፡ በተለይም ከ1997 ዓ.ም እስከ 2000 ዓ.ም መግቢያ ድረስ የታየው ለውጥ “ተአምራዊ” የተባለ ነበር፡፡ ይህ ወቅት የአልፋ “ወርቃማ ዘመን” ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ አኩሪ ውጤት መገኘት በወቅቱ የነበረው ቦርድ፣ የአልፋ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ማኔጅመንት የአመራር ብቃትና የሠራተኛው ታታሪነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ይሁንና ከ1999 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ግን የተለመደውና የተጠበቀው እድገቱ ሳይሆን የኋሊት ጉዞ ተጀመረ፡፡ ለዚህም ውድቀት መነሻ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን ፈጣን እድገት ማስቀጠል ያስችላል ተብሎ በባለሙያዎቹ ለ5 ወራት ያህል በጥንቃቄ የተጠናው የአደረጃጀት ማሻሻያና መዋቅር ተግባራዊ እንዳይሆን መደረጉ ነው፡፡ ሌላው በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ሰፊ እውቀትና ልምድ የነበራቸው መምህራንና ባለሙያዎች ተቋሙን ለቀው እንዲሄዱ በመደረጉ የዩኒቨርሲቲውን እንቅስቃሴ በእጅጉ ሊጎዳው ችሏል፡፡
በአሁኑ ዘመን ሕዝባችን የትምህርትና ሥልጠናን ጠቀሜታ በከፍተኛ ደረጃ ተገንዝቦ ቅድሚያ ራሱንና ቤተሰቡን በትምህርት ለማነጽ ያለውን አቅም ሁሉ ለመጠቀም ወደ ኋላ በማይልበት በአሁኑ ወቅትና ሌሎች በኪራይ ቤት ሠርተው አትራፊ እየሆኑ ባሉበት ሁኔታ የአልፋ ግዙፍ ሕንፃዎች ተማሪ አልባ ሆነው ማየት እንኳን ሀብቱንና እውቀቱን ላፈሰሰበት ባለ ሐብት ለተላላፊ መንገደኛም በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው፡፡
ለአክሲዮን ማህበሩ መውደቅ  “የመንግስት ፖሊሲ እና መመሪያዎች አላሰራም ማለት” እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ እውነቱ ግን ኩባንያው ያለውን የሰው፣ የቁሳቁስ እና የድርጅት ሀብት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ያለ መምራት ችግር ነው፡፡ ይህ ሁሉ አሳዛኝ ሂደት ያሳሰባቸው የተወሰኑ የአክሲዮን አባላት፣ የኩባንያው ፈጣን የቁልቁለት ጉዞ ያቆም ዘንድ ከአመራሩ ጋር ለመመካከር መድረክ እንዲመቻች በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ጥረታቸው ሰሚ በማጣቱ፣ የንግድ ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት 10% ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖችን ፊርማ በማሰባሰብ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ሰኔ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ሌላ የመደበኛና ድንገተኛ ጉባዔው ስብስብ በመጀመሪያ ነሐሴ 27 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡ ከዚያም እንደገና ይህ ውሣኔ ተሽሮ መስከረም 12 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲካሄድ ከተባለና አባላትም በተለያየ መንገድ ጥሪውን እንዲያውቁ ከተደረገ በኋላ፣ ለ3ኛ ጊዜ ሃሣባቸውን በመለወጥ፣ መስከረም 5 ቀን 2006 ዓ.ም ስብሰባው እንዲካሄድ በሪፖርተር ጋዜጣ ጥሪ ተደርጎ ነበር፡፡ ከእነዚህ የስብሰባ ቀናት መለዋወጥ መረዳት የሚቻለው፣ አመራሩ በኩባንያው ላይ የተከሰተውን ችግር በቅንነት ለመፍታት ልባዊ ተነሳሽነት እንዳልነበረው ነው፡፡
ጥሪው ከልብ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለምልአተ ጉባኤው አለመሟላት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ጥቂቶቹ፣ ጉባኤው የተካሄደበት እለት (መስከረም 5 ቀን) የአዲስ ዓመት መባቻ በመሆኑ አብዛኛው ባለ ሀብት ሊገኝ አለመቻሉ፣ ጥሪው በተገቢው ሁኔታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በሬዲዮን፣ በጋዜጦች፣ በፖስታ መልዕክትና፣ በሞባይል ስልክ መልዕክት አለመተላለፉ እና ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው የቦርድ አመራር አባላት ጭምር በጉባኤው ያለመገኘት የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በመሆኑም ሕጉ በሚያዘው መሠረት ድጋሚ መጠራት የነበረበት ጉባኤ፣ በ15 ቀናት ውስጥ እንዲካሄድ የተደረሰው ስምምነትም ተግባራዊ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴውም አቤቱታውን ለሚመለከተው የመንግስት መ/ቤት በወቅቱ አቅርቧል፡፡ አቤቱታ የቀረበለት የንግድ ሚኒስቴርም ስብሰባው ለምን በስምምነቱና በደንቡ መሠረት እንዳልተካሄደ ቦርዱን ጠርቶ ማብራሪያ እንዲሰጠው በጠየቀ ጊዜ “ወጪ ለመቀነስ ስለታሰበ” መደበኛውንና ድንገተኛ ጉባዔውን በማጣመር ማስኬድ በማስፈለጉ እንደሆነ ተገልጾለታል።በእርግጥ ስብሰባው ከዓመታዊ ጉባዔው ጋር ተጣምሮ እንዲካሄድ የተወሰነው “ወጪ ለመቀነስ ነው” የሚለው አካል፣ ለአልፋ ገንዘብ ቁጠባ አሳቢ ቢሆን ኖሮ፣ በርካታ ሊቆጠቡ የሚገባቸው ወጪዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ግን ይህን ሀሳብ ተቀብሎ ጉባዔዎቹን በጥምር ማካሄድ እንደሚቻል፣ ነገር ግን የቅሬታ አቅራቢዎቹ አጀንዳዎች ያደሩ  በመሆናቸው በቅድሚያ ቀርበው ከታዩ በኋላ፣ የቦርዱ አጀንዳ እንዲቀርብ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ይሁንና ቦርዱ የተደረሰውን ስምምነት እንደገና በማፍረስ የጠቅላላ ጉባኤውን ህዳር 15 ቀን 2006 ዓ.ም ለማካሄድ ባደረገው ጥሪም እና በዚህ ጥሪ ላይ በቀረፀው አጀንዳ ላይ አስተባባሪ ኮሚቴው ያቀረበው አንዱ አጀንዳ ብቻ (በ1.6ኛ ተራ ቁጥር ላይ ያለው) የተቀመጠ ሲሆን ሌላው የድንገተኛ ጉባኤ አጀንዳ ግን ጭራሽ አለመቅረቡን ጥቅምት 30 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መመልከት ይቻላል፡፡ ይህንንም ሁኔታ አስተባባሪ ኮሚቴው ለንግድ ሚኒስቴር እንደገና በአቤቱታ መልክ በማቅረብ፣ የቅሬታ አቅራቢ ባለአክስዮኖች አጀንዳ በቅድሚያ እንዲታይ ለቦርዱ ጥብቅ ትዕዛዝ ጽፏል፡፡ ይህ ጥብቅ ማሳሰቢያ ወደፊት በተሰጠው ማሳሰቢያ መሰረት የሚተገበር መሆን አለመሆኑን እድሜ ከሰጠን የምናየው ይሆናል፡፡
ውድ የተከበራችሁ የአልፋ ትምህርትና ሥልጠና አ.ማ ባለአክሲዮኖች፡- አክስዮን ማኅበራችንን ለማሳደግና ተጠቃሚ ለመሆን በዕውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ ተገቢውን ሁሉ ፈጽመን አንቱ የተባለ ኩባንያ መመስረት ችለን እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ሁኔታዎች ሁሉ በሚፈለገው መንገድ እየሄዱ ባለመሆኑ፣ ሁሉም ባለ አክሲዮኖች ህዳር 15 ቀን 2006 ዓ.ም እንደሚካሄድ በወጣው ማስታወቂያ መሠረት፤ በስብሰባው ላይ በመገኘት በአክሲዮን ማህበሩ ችግሮች፣ መንስኤዎችና መፍትሄዎቻቸው ላይ በዝርዝር በመነጋገር በቀጣይ መወሰድ ስላለበት እርምጃ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ ማድረግ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ (ከቅሬታ አቅራቢ ባለአክሲዮኖች አስተባባሪ ኮሚቴ)  

Published in ባህል

እንዴት ከረማችሁሳ!
ስሙኝማ…ይሄ አሥር በመቶ እውነት፣ ዘጠና በመቶ ሽወዳ በሆነበት የነጻ ትግሉ (WWE) ክትክት ላይ  “ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” (“It’s good for business”) የሚሏት ነገር አለች፡፡ ያው ለ‘ቢዙ’ አሪፍ ነገር ማለት ነው፡፡
እናም…በዚህ በኳሳችን ብሔራዊ ስሜትንና “ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” እየተደበላለቀ ሕዝቤ ደህና ንግዱን ሲያጧጡፍ ከረመ፡፡ በየመንገዱ ቀለም መቀባቱ፣ ካናቴራ፣ ስካርፍ፣ ኮፍያ፣ ባርኔጣ ምናምን መሸጡ በአብዛኛው የ‘ቢዙ’ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ‘ግርግር’ ሙሉ ለሙሉ እንደ ብሔራዊ ስሜት መግለጹ አሪፍ አይደለም፡፡
ስለ ቡድኑ በየኤፍኤሙ እንሰማቸው የነበሩ የሚያስገርሙ፣ አንዳንዴም የሚያስደነግጡ፣ ዘገባዎች… አለ አይደል… እውነተኛ አቋማችን ሆኖ ሳይሆን ነገርዬው “ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” ነው። አሀ…የስፖንሰር ጉዳይ ነዋ! ስፖንሰሮች ደግ፣ ደግ እንዲወራ ይፈልጋሉዋ! የቡድኑ እዚህ መድረስ “የእንትናችን ውጤት ነው…” እየተባለ ነዋ!
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንዳንድ ዘገባዎች ‘ልማታዊ የስፖርት ዘገባዎች’ አይነት ሆኑብንሳ! (ስሙኝማ… ‘በቀጥታ ስርጭቱ’ ጊዜ በተደጋጋሚ “የእጅ ውርወራ” “የመልስ ምት” እየተባለ ሲጠቀስ ምን አልኩ መሰላችሁ…ፊፋ ሰሞኑን የለዋወጣቸው ህጎች አሉ እንዴ? ግራ ሲገባኝስ!)
ስሙኝማ…ይሄ የዳኝነት ነገር አስቸጋሪ ነው። የበቀደሙ ዳኛ ሆነ ብሎ በማዳላትም ይሁን፣ ‘ኢኖሰንት ሚስቴክ’ የሚሉትም አይነት ቢሆን አንዳንድ ነገር ላይ የተጫኑን ይመስላል፡፡ የዳኝነት ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ፡፡
ሦስት በዕድሜ የገፉ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ለየቡደኖቻቸው እየጸለዩ ነው፡፡ አንደኛው ደጋፊ እንዲህ ይላል… “እግዚአብሔር ሆይ፣ ማንቼስተር ሲቲ ለዳኞች ጉቦ መስጠት የሚያቆመው መቼ ነው?”
“በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት” ሲል እግዚአብሔር ይመልሳል፡፡
ሰውየውም “እስከዛማ እኔ እሞታለሁ” ይላል፡፡
ሁለተኛው ደጋፊ እንዲህ ይላል… “እግዚአብሔር ሆይ፣ ማንቼስተር ዩናይትድ ለዳኞች ጉቦ መስጠት የሚያቆመው መቼ ነው?”
“በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት” ሲል እግዚአብሔር ይመልሳል፡፡
ሦስተኛው ደጋፊ እንዲህ ይላል… “እግዚአብሔር ሆይ፣ ባርሴሎና ለዳኞች ጉቦ መስጠት የሚያቆመው መቼ ነው?”
እግዚአብሔር ምን ቢል ጥሩ ነው፣ “እስከዛማ እኔ እሞታለሁ፡፡”
እናማ…በተከታታይ ዳኞች ጎል በመከልከልና በጣም፣ እጅግ በጣም አጠያያቂ ፍጹም ቅጣት በመስጠት የተጫኑን ሆነ ተብሎ ይሁን የችሎታ ማነስ ወይም ሌላ አንድዬ ይወቀው፡፡  
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንድ ግዙፍ የስፖርት ሚዲያ በድረ ገጹ የኢትዮዽያን ቡድን አድንቆ ናይጄሪያን ሊያሸንፍ እንደሚችል ጻፈ የሚባል ነገር በአንዱ የእኛው ሜዲያ ሰማሁላችሁና ወዲያውኑ ተጻፈበት የታበለለትን ድረ ገጹን አየሁት። እናላችሁ… ስለ ጨዋታው ያወራና መጨረሻ ምን ይላል መሰላችሁ… “Definitely the African champions will finish off the Ethiopians in Calabar this Saturday and book their place at the 2014 Fifa World Cup in Brazil.”
ምንም ‘የፈረንጅ አፍ’ ቢቸግረን ይቺ አትጠፋንማ! ናይጄሪያ “በእርግጠኝነት…” ቡድናችንን እንደሚያሸንፈው የሚናገር መሰለኝ። (“‘የፈረንጅ አፍ’ እንደፈቺው ነው…” ተብሎ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
እናማ “ዓለም አደነቀን…”፣ ወይም “ዓለምን እያስደመመን ነው…” እየተባለ ድረ ገጾች ያልጻፉት ነገር እንደጻፉት ሲነግሩን የሰማንባቸው ጊዜያት አሉ። ምክንያቱም እንደዚሀ አይነት አዘጋጋብ “ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” …አንደኛ ስፖንሰር አያስከፋም፣ ሁለተኛ ልማታዊ ነገርም ይሆናል፣ ሦስተኛ የኔኦ ሊበራሊስቶችን ወሽመጥ ይበጥሳል! ቂ..ቂ…ቂ…፡፡
እናላችሁ… ብሔራዊ ስሜት የሚያስፈልግባቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ለብዙ ችግሮች ያጋለጠን የብሔራዊ ስሜት መጥፋት ነው፤ እርስ በእርስ መደማመጥ ያቃተን የብሔራዊ ስሜት መጥፋት ነው፣ ዘረኞች ያደረገን፣ ጎጠኞች ያደረገን “በእርግጠኝነት” የብሔራዊ ስሜት መጥፋት ነው። ሁሉን ነገር በአመቻ ጋብቻ እንድንሠራ እያደረገን ያለው የብሔራዊ ስሜት መጥፋት ነው፡፡ በአገሪቷ የልጅና የእንጀራ ልጅ አይነት አገልግሎት አሰጣጥ ባህል እንዲሆን ያደረገው የብሔራዊ ስሜት መጥፋት ነው፡፡ እናማ… በአንድ ልብ ማሰብ፣ በአንድ ድምጽ መጮህ ምን ያህል እንደሚያረካ ‘ሳምፕሉን’ እንድናይ ላደረገን ብሔራዊ ቡድናችን ምስጋና ይግባው!
ስለ ብሔራዊ ስሜት ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…የኤፍ.ቢ.አይ. ሰዎች ሰላይ ለመቅጠር ሦስት ዕጩዎችን በተናጥል ቃለ መጠይቅ እያደረጉ ነው፡፡
የመጀመሪያውን ሰው “ሚስትህን ትወዳለህ?” ተብሎ ይጠየቃል፡፡
“አዎ፣ ጌታዬ እወዳታለሁ”
“አገርህን ትወዳታለህ?”
“ከሚስትህና ከአገርህ ይበልጥ የምትወደው የትኛዋን ነው?”
ከዛ ሽጉጥ ይሰጠውና “እንግዲያው፣ ሚስትህ የሚቀጥለው ክፍል ነች ግባና ግደላት” ይባላል። ሰውየውም ሽጉጡን ያስቀምጥና “ይሄን እንኳን ማድረግ አልችልም…” ብሎ ወጥቶ ይሄዳል፡፡
ሁለተኛው ሰው ተመሳሳይ ጥያቄዎች ይቀርቡለትና ሽጉጥ ይዞ ሚስቱ ያለችበት ክፍል ይገባል፡፡ ለአምስት ደቂቃ ቆይቶ ይወጣል፡፡ “ይህንን እንኳን ማድረግ አልችልም…” ብሎ ሽጉጡን አስቀምጦ ይሄዳል፡፡
ሦስተኛው ሰው ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበውለት ሽጉጥ ይዞ ይገባል፡፡ የታፈኑ የተኩስ ድምጾች ይሰማሉ፡፡ ጥቂት ቆይቶ የመንኳኳት ድምጾች ይሰማሉ፡፡ ከዛም ሰውየው ከረባቱ ላልቶ፣ የሸሚዙ እጅጌዎች ተሰብስበው ከክፍሉ ይወጣል፡፡ ሽጉጡንም ጠረዼዛው ላይ ያስቀምጣል፡፡
ቃለ መጠይቅ አድራጊዎቹም “ምን ተፈጠረ?” ብለው ይጠይቁታል፡፡
ሰውየው ምን አለ መሰላችሁ… “ጥይቶቹ የውሸት ስለነበሩ በእጄ አንቄ ገደልኳት፡፡”
ሚስትን አንቆ ‘ጭጭ የሚያስደርግ’ ባይሆንም ትንንሽ እንጥፍጣፊ ብሔራዊ ስሜት ብዙ በጎ ነገሮች ለማድረግ የሚያግዝ ይመስለኛል፡፡
እናማ…ከዚህ በፊት እንዳወራነው የዘንድሮ ብሔራዊ ቡድናችን ሁላችንም ለአንድ ጉዳይ እኩል እንድንጮህ አድርጎናል፡፡ የበይ ተመልካች ሆነን የኖርንበት ዓለም ዋንጫ ደጃፍ ደርሰን በሩን እንድናንኳኳ አድርጎናል፡፡ ታፔላ ሳንለጣጥፍ፣ ሳንወጋገዝ፣ “ቡድኑን እንዲህ የሚሉት የራሳቸው ዓላማ ያላቸው…” ምናምን ሳንባባል…እኩል “ሆ!” እንድንል አድርጎናል፡፡ አ
ንድዬ ይሄን አይነቱ ጸጋ በሁሉም ነገሮች ላይ እንዲገጥመን ያድርግልንማ!
ምስጋናና ክብር ለብሔራዊ ቡድናችን!
አንድዬ ደግሞ በር አንኳኩቶ የሚመለስ ብቻ ሳይሆን በሩን አስከፍቶ የሚገባ ቡድንም እንዲኖረን ይርዳንማ፡፡ እንዲህ አይነቱን ቡድን ለማየት ዕድሜና ጤናውን ያድለንማ!
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…አንድ መልዐክ ይመጣና አንዱን ሰውዬ “የምትፈልገውን አንድ ምኞት ንገረኝና አስፈጽምልሀለሁ! ይለዋል፡፡ ሰውየውም “ለዘለዓለም መኖር እፈልጋለሁ” ሲል ይመልሳል፡፡ መልዐኩም “አዝናለሁ፣ እንደዛ አይነት ምኞቶችን የመፈጸም ስልጣን አልተሰጠኝም፡፡”
ሰውየውም ምን ይላል “እሺ፣ እንደዛ ከሆነ ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲበላ መሞት እፈልጋለሁ፡፡”
መልዐኩ ሳቅ ብሎ ምን ቢለው ጥሩ ነው… “በጣም ብልጥ ነህ፣ ለብዙ አሥርት ዓመታት መኖር ትፈልጋለሀ ማለት ነው፡፡”
ትልቁ የእግር ኳስ አደባባይ ለመገኘት ለብዙ አሥርት ዓመታት ከመጠበቅ ያድነንማ!
ደግሞላችሁ… ሁሉም ነገር “ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” እየተባለ መቀባባትና መኳኳል ከቀጠለ የመልዐኩ “በጣም ብልጥ ነህ…” ነገር አይለቀንም፡፡
 ሦስት ደጋፊዎች ውጤት ማምጣት ስላቃተውና ስለሚደግፉት የከተማቸው ቡድን እያወሩ ነበር፡፡
አንደኛው ምን ይላል…“ጥፋቱ የአሰልጣኙ ነው፣ የተሻሉ ተጫዋቾች ቢያስፈርም ኖሮ ቡድናችን ትልቅ ይሆን ነበር፡፡”
ሁለተኛው ደግሞ “ጥፋቱ የተጫዋቾች ነው፡፡ የተሻለ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ ብዙ ጎሎች እናስቆጥር ነበር” ይላል፡፡ሦስተኛው ደጋፊ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ጥፋቱ የወላጆቼ ነው፣ ሌላ ከተማ ወልደውኝ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ቡድን ደጋፊ እሆን ነበር፡፡”
እናላችሁ…የትም እንወለድ የትም ትልቅ የነበረች አገር ዜጎች ነንና…ትልቅ መሆን የምትችል አገር ዜጎች ነንና…ይዋል ይደርም ወደ ትልቅነቷ የምትመለስ አገር ዜጎች ነንና… ብሔራዊ ቡድናችን የተሻለ ሆኖ ለማየት ያብቃንማ!
ብሔራዊ ስሜት…አለ አይደል…“ኢትስ ጉድ ፎር ቢዝነስ” ከሚለው ዳሌን የማስፋትና ሻኛን የመከመር ‘ሆድ—ተኮር’ አስተሳሰብ የላቀ መሆኑን አንድዬ በየልቦናችን ያስርጽብንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

           ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የመዝገቡ ተሰማ ስዕሎችን የማየት እድል ያገኘሁት፡፡ በህይወት ከምናያቸው ማራኪ መናፈሻ ስፍራዎች ሁሉ ያማረና የለምለም ድንቅ መስክን በምናባችሁ አስቡ፡፡ አድማስ ድረስ የሚዘልቅ የሚመስልና መንፈስን የሚያዝናና አረንጓዴ መስኩ ላይ ደግሞ፤ በአካል ከምናያቸው ውብ ቆነጃጅት ሁሉ የላቀች ለግላጋ ወጣት! ከመቅጽበት በፍቅር የምትማርክና ልብን የምታንጠለጥል ይህችው የውበት ልዕልት፣ ለምለሙ ሳር ላይ ጋደም ብላ በጉጉት እና በናፍቆት ስሜት… የሷም ልብ ተንጠልጥሎ ፍቅርን ትጠብቃለች…
ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁትን የመዝገቡ ስዕል በቃላት ለመግለጽ እየሞከርኩ እንደሆነ ተረዱልኝ።  አይኔን መንቀል ፈተና እስኪሆንብኝ ድረስ ተደነቅሁ። ግን ሌሎቹን ድንቅ ስዕሎቹንም ማየት ነበረብኝ፡፡ በየእለቱ ከምናየው ወይም ከምናውቀው ውበትና ማራኪነት ሁሉ የላቀ ውበትን በእውን ሰርቶ እያሳየ፣ እኛው ከፍ እና ላቅ አድርገን እንድናስብ የሚያደርግ ድንቅ ሰዓሊ ነው መዝገቡ፡፡ በእለት ተእለት የኑሮ ሩጫም ሆነ በቸልታ ጥቃቅን ነገሮች ላይ ስናተኩር ትልልቅና ቁልፍ የህይወት ቁም ነገሮችን መመልከት ይሳነን የለ? ነገር አለሙ ሁሉ ይደበዝዝብናል ወይም ብዥ ይልብናል፡፡ የህይወትን አልማዞችና ወርቆችን እያጠራና እያነጠረ አጉልቶ ያሳየናል - በስዕሎቹ ነፍስ እየዘራባቸው፡፡ እናም “ለካ እንዲህ አይነት ውበትም አለ” እንድንል የሚያደርግ ብርቅ ሰዓሊ ነው - መዝገቡ፡፡
በአጭሩ ከመዝገቡ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ፍላጐቶችን የሚያሟላ፣ የህይወት ማዕድ የሚያሰናዳ ጥበበኛ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል፤ ስዕሎቹን የተመለከቱ በርካታ ሰዎች “አይኖችህ የተባረኩ፣ እጆችህ  የተቀደሱ፣ ሥራዎችህ የመጠቁ ናቸው” ሲሉ የሚደመጡት፡፡ የመጀመሪያው መንፈሳዊ ፍላጐት፣ በተለምዶ “አለምን የማወቅ ጉጉት” እንለዋለን፡፡ ተፈጥሮን አጥርቶና አንጥሮ ማየት ይቻላል የሚል የአእምሮ አለኝታነትን የሚያረጋግጥ መንፈስ ያላብሰናል፡፡
የመዝገቡ ተሰማ ስዕሎች ላይም የጠራ የነጠረ አለምን ነው የምናየው፡፡ የነጠረና የተመረጠ አለምን እንጅ የቅራቅንቦ ስብስብ ምስቅልቅልን አያቀርብልንም፡፡ የጠራ የጐላ አለምን ይጋብዘናል እንጂ በብዥታ የተጋረደ ሌጣና ኦና አለምን አይግተንም፡፡ ሁለተኛው መንፈሳዊ ፍላጐት፤ በለምዶ ራዕይ ወይም ፍቅር ብለን እንጠራዋለን። ወደ ከፍታ የመምጠቅ ጉጉትን የሚያገናኝ፣ እውቀትንና ስኬትን የሚያስተሳስር፣ አእምሮንና አላማን የሚያዛምድ ነው፡፡
ሦስተኛው መንፈሳዊ ፍላጐት - የላቀ ብቃትንና የላቀ ስብዕናን መቀዳጀት የምችል ሰው ነኝ የሚል የእኔነት ክብር፡፡ መዝገቡ ተሰማ አረንጔዴ ስፍራ ሲስል፤ ከተለመደው ሁሉ የላቀ ልምላሜን ያላብሰዋል፡፡ ሴቶችን ሲስል ከለግላጋ ማራኪነት የላቀ ፍቅርን የሚጓጉ፣ ከፍ ያለ ደስታን የሚናፍቁ አድርጐ ይቀርፃቸዋል፡፡ የተራራ አናት ላይ ያወጣቸዋል፡፡ ወደፊት ወደ ላይ እየተንጠራሩ ለመብረር እንዲያኮበኩቡ ያደርጋቸዋል፡፡  
እናም የመዝገቡን ስዕሎች ያየሁ ጊዜ፣ “ከዚህ የበለጠ ድንቅ ስራ ከወዴት ይመጣል” ብዬ ተደነቅሁ። በእርግጥም የበለጠ ነገር አላየሁም፡፡ ማለቴ ለጊዜው አላየሁም፡፡ መዝገቡ ተሰማ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በ1996 ዓ.ም በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ፣ አዳዲስ የስዕል ስራዎቹን ለእይታ ያቀረበ ጊዜም፤ ከቀድሞ ድንቅ ስራዎቹ ጋር የሚመጣጠኑ ፈጠራዎችን ለማየት ተስፋ በማድረግ ነበር የሄድኩት፡፡
ግን እንደጠበቅኩት አልሆነም፡፡ ከቀድሞ ስራዎቹ የሚበልጡና የሚልቁ ድንቅ ስዕሎችን ነው ያቀረበው፡፡
በአዳራሹ አንድ ወገን፣ የማታውን ጨለማ ለመግፈፍና ለማባረር የተፈጠረ፣ ፍም የመሰለ የንጋት ብርሃን አየሁ - በትልቅ ሸራ ላይ የተሰራ ስዕል ነው፤ የህይወት ሃያል የማለዳ ብርሃን፡፡ ከወዲያ ማዶ ደግሞ፤ የዚያኑ ያህል የአዳራሹን ግድግዳ የሚሸፍን ስዕል ይታየል - ቀኑን ተሰማርተው የዋሉና የሚያምሩ ከብቶች… ከላሚቱ አጠገብ እመር የምትል ጥጃ፣ በግርማ ሞገስ የሚራመዱ ኮርማዎችና በሬዎች … በየራሳቸው መልክና ቀለም፣ አመሻሽ ላይ እያዘገሙ እየተመለሱ ይመስላሉ፡፡ በእለት ተእለት ከምናያቸው ከብቶች ሁሉ ይበልጥ የሚማርኩ፣ በየአጋጣሚ ከምናየው የከብቶች ስምሪት ሁሉ የሚያምሩ ትዕይንቶችን ከበርካታ የመዝገቡ ተሰማ ስዕሎች ላይ እንመለከታለን፡፡
ከዚሁ አጠገብ የነበሩት ሁለት ግዙፍ ስእሎችም ድንቅ ናቸው፡፡ ከግራ በኩል የነበረው ስዕል አረንጓዴ መናፈሻ ይመስላል፡፡ እርግት ያለው ልምላሜ ፍፁም ሰላም የሰፈነበት ከመሆኑ የተነሳ፣ ምናልባት “ገነት” የሚባለው ስፍራ  እንዲህ ይሆን እንዴ? ያስብላል፡፡ ሁለት እምቦቃቅላ ጨቅላዎች ከመስኩ መሃል ምቹ መኝታ ላይ፤ ከራስጌና ከግርጌ ተጠጋግተው አንቀላፍተዋል፡፡  ሌላኛው ግዙፍ ስዕል፤ ተራራ ላይ ከሚገኝ ጨለምለም ያለ ሰፊ ዋሻ ውስጥ ቁልቁል እስከ አድማስ ጥግ በብርሃን የተጥለቀለቀ ዛፍና ቅጠሉን፣ መስክና ጐጆውን፣ ኮረብታና ሸንተረሩን ሁሉ የሚያሳይ ነው፡፡ ፎቅ ላይ ወይም ሌላ ከፍተኛ ቦታ ላይ ስትወጡና ወደታች ስትመለከቱ የሚፈጠረው ስሜት ታውቁት የለ? ይህንን የመዝገቡ ስዕል ስትመለከቱም ተመሳሳይ ስሜት ጐብኝት ያደርጋችኋል፡፡  ከስዕሉ የቅንብር ጥበብ የመነጨ ውጤት ነው፡፡
የቁልቁለት የዳገቱ፣ የኩርባ የገደሉ፣ የማሳ የመንደሩ ምስል ንጥር -ጥርት ያለ ቢሆንም አቀማመጥና ቅንብሩ የአሽከርካሪት ባህርይ አለው። ከከፍታ ቦታ ሆነን ስንመለከት የሚፈጠርብን አይነት ስሜት፡፡ መዝገቡ ተሰማ፣ በቀለም አዋቂነቱ የላቀ ድንቅ ሰዓሊ መሆኑ ባያከራክርም በቅንብር ችሎታውም ወደር የሚገኝለት አይመስልም፡፡ በዚያን ወቅት በ1996 ዓ.ም በኤግዚቢሽኑ ካቀረባቸው ስዕሎች መካከል፣ “አድባር” የሚል ርዕስ የሰጠው ስዕልም የመዝገቡን የቅንብር ችሎታ ይመሰክራል፡፡
እንደሰማይ የራቀ የተራራ ጫፍን አጉልቶ እያሳየ፣ በዚያው መጠን ከታች አረንጓዴ የእርሻ ማሳና መኖሪያ መንደሮችን አስፍቶ ያሳያል ስዕሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ከተራራው ጫፍ ወደ ጐን ገፍቶ የወጣ ቀጭን አለት ላይ አንዲት መልከ መልካም ወይዘሪት  ቆማለች - ከምድር ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ርቃ፡፡ ዘና ብላ ነው አፋፍ ላይ የቆመችው፡፡ ውቧ እና ማራኪዋ “አድባር” የትኛውም ከፍታ ላይ መውጣት ትችላለች፡፡ የማይቻላት ነገር፤ የማትደርስበት ከፍታ የለም፡፡ የተራራ አናት አፋፍ ላይ የቆመችን ሴት አጉልቶ፤ ወደ ታች ለማሳየት ድንቅ የቅንብር ጥበብን ይጠይቃል፡፡
ሰማይ ጠቀስ የተራራ አናት ላይ ዘና ብላ የቆመችን ሴት አጉልቶ፣ በጣም ታች ታች ያለው መንደሮችና ማሳዎችንም አስፍቶ ለማሳየት፤ ልዩ የቅንብር ጥበብን ይጠይቃል - በሌላ አነጋገር የመዝገቡን አይነት የቅንብር ጥበብ መካን ያስፈልጋል፡፡  
መዝገቡ ከከፍታ ጋር ልዩ ፍቅር ያለው ይመስላል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተከፈተው ኤግዚቢሽን ያቀረባቸው ስዕሎችም፤ “ከፍታ”ን እና “ልቀት”ን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡
“ላየን ኪንግ” የተሰኘውን ድንቅ ፊልም ታስታውሱት ይሆናል፡፡ የጫካው ንጉስ ታላቁ አንበሳ፤ በከፍታ ገንኖ ከሚታይ አለት ጫፍ ላይ ወጥቶ፣ በነጐድጓድ ድምጽ እያገሳ፣ ህልውናውን ለመላው አለም ሲያውጅ የሚታይበት ቦታ አለ፡፡ ያንን አይነት ስሜት የሚያሳድር ነው አንዱ የመዝገቡ ስዕል፤ “ከፍታ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
“ህልመኛ” በሚል ርዕስ ያቀረበው ሌላኛው ግዙፍ ስዕልም እንዲሁ፤ “ከፍታ”ን አቅርቦ የሚያሳይ ነው፡፡ በአስገራሚ ሁኔታ የተደራረበና የተነባበረ አለት፣ በሃይቅ ዳርቻ ላይ ያንዣበበ ይመስላል፡፡ ከታች የሃይቁ ውሃ ያንፀባርቃል፡፡ ከላይ ከፍታው አናት ላይ ደግሞ፣ ልብስ ያላደረገ ልጅ ይታያል። በኤግዚቢሽኑ ከቀረቡት 15 ስዕሎች፤ በጣም ትንሿ በአንድ ሜትር  ሸራ የቀረበችው ስዕል ናት፡፡ በሳር መስክ የተከበበችና ሸብረክ ብላ የተቀመጠች ብቸኛ ግልገል! መዝገቡ የራሱን ችሎታ ለመፈተን የሰራው የሚመስለው “ላል” የተሰኘውን ስዕል ጨምሮ ስዕሎቹ በሙሉ ድንቅ የጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ተለይተው ሊጠቀሱ ይገባቸዋል የምላቸውን አምስት ስዕሎች አይቻለሁ፡፡
ወደ አዳራሹ ሲገባ በስተግራ የምናገኘው የመጀመሪያው ስዕል፤ “ግለት” የተሰኘና የእሳተ ጐመራ ስፍራ የሚመስል ስዕል ነው፡፡ “እንዲህ አይነት እቶን እና ፍም ታይቶ ይታወቃል?” ያሰኛል፡፡ እውነትም “ግለት” ይሉሃል ይሄ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ “ምቹ ቦታ” የሚል ርዕስ የተሰጠው ስዕል ነው፡፡
ከቅርበትና በስፋት ጐልቶ ከሚታየው ሜዳና ተራራው፣ ጋራና ሸንተረሩ ባሻገር፣ ከተራራ ጀርባ ሌላ የተራራ ሰንሰለት፤ ከዚያ ጀርባ ደግሞ ሌላ ተራራ… ለአይን እስኪያስቸግር ድረስ በተዘረጋው በዚያ ቦታ ላይ በአካል መገኘትን የሚያስመኝ ስዕል ነው፡፡
ሌሎቹ ሦስት ስዕሎች ለብቻቸው ልዩና የላቀ ደረጃ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ለምን ቢባል፣  “የተዘረጋ” እና “እሷና ሌሎች” በሚል ስያሜ የቀረቡት ሥራዎች፣ የስዕል ጥበብ ላይ ተጠቃሽ እመርታን የሚያስመዘግቡ ናቸው፡፡ ከቀለም፣ ከብርሃንና ከቅንብር ጥበቦች በተጨማሪ፣ አዳዲስ ጥበቦችን በመጠቀም ለምስሎቹ ልዩ ጥልቀትንና ግዝፈትን አጐናጽፏቸዋል፡፡ ሸራው ጠፍጣፋ ነው፡፡ ምስሎቹ ግን፣ ከሸራው ጀርባ ብዙ ኪሎሜትሮችን ጠልቀውና ሰፍተው የሚዘረጉ፣ ከሸራው ፊትም ተመልካችን ለመንካት የሚመዘዙ ይመስላሉ፡፡ የስዕልን “3D” ባህርይ እንዲህ አጉልቶ ያወጣ የአገራችን ሰዓሊ የለም፡፡
“ንግሥ” የተሰኘው ስዕል ደግሞ፤ የኤግዚቢሽኑ ንጉስ ነው ማለት ይቻላል፡፡ 5 ሜትር በ2 ሜትር ስፋት ላይ የቀረበውና ከ160 በላይ የሰው ገፀ ባህርያትን ገልጦ የሚያሳየው ይሄው ስዕል፣ ግርማ ሞገስን፣ አክብሮትን፣ ስነ ሥርዓትን፣ በአጠቃላይ የሰው ልጅ ለትልቅነት ወይም ለቅድስና ያለውን ጉጉት የሚያሳይ ታላቅ ሥራ ነው - እጅግ ታላቅ ሥራ፡፡   

Published in ህብረተሰብ

“ይህ ማህበር የጄክዶ ልጅ ነው ለማለት ይቻላል!”
(በድሬዳዋ አስ/ማብ -መር የአደጋ ቅነሳ አየበጐ አድራጐት ማህበር የፕሮጄክት ኦፊሰር)
*   *   *
“ድሬዳዋ፤ ያለምንም መግቢያ የተፃፈ ድርሰት ናት!”
 *   *   *
ድሬዳዋ ድንገት ገብተህ ድንገት የምትወጣባት ከተማ ናት”
*   *   *
“ድሬዳዋ ኮሙኒቲ አክሽን” (DDCA) “የማህበረ ሰብ ተሳትፎ ዘላቂ ልማትን ያረጋግጣል”
*   *   *

ባለፈው ዕትም የጉዞ ማስታወሻዬ በድሬዳዋ የጐርፍ መከላከል ሥራ ከእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ድርጅት ጋር እንዴት እንደተጀመረና የመንደር ኮሚቴዎች መመሥረታቸውን በማውሳት ላይ ነበር ያቋረጥኩት፡፡ እንቀጥል፡፡
ከአራቱ ቀበሌዎች ዘጠኝ ዘጠኝ ሰው ሰላሣ ስድስት አመራር ተመሠረተ፡፡ በጥናቱ መሠረት የአፈርና ውሃው ሥራ ከእየሩሣሌም ጋር ተጀመረ፡፡ የአጭርና ረዥም ጊዜ ዕቅድ ታቀደ፡፡
ለመስተደድሩ ፔቲሽን ቀረበ፡፡ ከማዕከላዊ ኮሚቴው ለከንቲባው የቀረበው ተቀባይነት አገኘ፡፡ መንግሥትም ገባበት፡፡
በተደረገው መረባረብ ከ1998 ቀጥሎ የመጣው ጐርፍ ጉዳት ሳያደርስ ቀረ፡፡ ጥንቃቄው ውጤት የተገኘበትና መቀነስ/መከላከል እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ሆነ፡፡ ከ36ቱ ሥራ አመራር አባላት ብርቱ አቅም ተፈጠረ፡፡ ሥልጠና ቀጠለ፡፡ አደረጃጀቱ ቀጠለ። ቦርዱ በ7 አባላት ተቋቋመ፡፡ የመግባቢያ ሰነድ ረቆ ለፍትሕ ሚ/ር ለዕውቅና ተሰጠ፡፡ በፌዴራል ማህበራት ማደራጃ ኤጀንሲ ዕውቅና አገኘ፡፡ ጄክዶ አንድ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ሰጠን፡፡ ዕውቅና ሐምሌ 19 2002 ላይ አገኘን። የአሠራር ልምዱን ለ38 የገበሬ ማህበራት ለማጋራት ተንቀሳቀስን፡፡ ጐርፉ፤ ከጠንገጐ ጀምሮ እስከ ቀርሳና ቁልቢ ያለው ቦታ ነው ዋና መነሻው፤ በጋራ ሥርዓት ዘይቤ የገጠርና የከተማ ቅንጅት ወርክሾፕ ተዘጋጀ።  መረብ የመዘርጋትና የቅድመ - ዝግጅት ሥርዓት፣ አርጌሌና ገንዳ አርአያ በሚባሉ ቦታዎች ላይ ነው፡፡”
“ያጋጠማችሁ ችግርስ አልነበረም ወይ?” አልኳቸው።
“በመጀመሪያ ጐርፉ ሲያንስ ሰው ‘እንቅልፍ ነሱን’ ይል ነበረ፡፡ በኋላ ግን ገባው፡፡
ጐርፉን ቀልብሰው ማሽላና በቆሎ ነው የሚዘሩት። ከፍተኛ ውጤት ያለው ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይቀለበሳል። ማሽላ ይሆናል፡፡ ገበሬዎቹ ያውቁታል፡፡ ልጆቻቸው ወላጆቻቸው እዚህ ነው የሚነግዱት፡፡ መተሳሰብ አለ። ለዘለቄታው በችግኝ ተከላ ለመከላከል እንደሚቻል ያውቃሉ፡፡ በዕቅድ ተይዟል፡፡ ከጄክዶ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን በቅንጅት እንሠራለን፡፡ በዚህ 2 ዓመት ይሄን ቤት ተከራይተናል በቦርድ ይመራል፡፡ ምንም ፈንድ ስላልነበረን በቅርብ ሆኖ የፈንድ እገዛ ያደራጀልን ጄክዶ ነው፡፡ ኪራይ፣ ውሃ፣ መብራት፣ በትራንስፖርት፤ በሙያ አግዞናል፡፡ የአፈር እና ውሃ፣ የእርከን፣ የክትር፣ የቅልበሳ፣ የጋራ ትብብር ከሌሎች ጋር እንሠራለን፡፡ ማህበረሰቡ በባለቤትነት ተረክቦ ይመራዋል በመጨረሻ፡፡”
“የበጐ ፈቃደኝነት ነገርስ ችግር የለውም?” አልኳቸው፡፡
“ያለትራንስፖርት አበል በበጐ ፈቃደኛነት ስለምንሠራ
ህዝቡ አክብሮት አለው፡፡
ጥቅም ቢኖረው ተሻሚዎች ይኖሩ ነበረ፡፡ መቀጠሉ
ራሱ የሚደነቅ ነው!
አልፎ አልፎ ባለሙያው በፈቃዱ ሙያውን መስጠቱ ይታገለዋል፡፡ ያም ሆኖ  የዕውቀት እጥረት ድሀውን ይመታል፡፡ አዲስ ከመሆናችን አንፃር አንዳንድ ክፍተት ከመታየቱ በስተቀር አመርቂ ሥራ ሠርተናል ብዬ አምናለሁ፡፡ የሴቶች ድርጅት አለን፡፡ መዋጮን ማጠናከር አንዱ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ ባለድርሻ አካላት የእኛ ነው እንዲሉ ማድረግ፡፡ ትልቁ ችግር የወጣቱ የበጐ ፈቃደኝነት ማነስ ነው፡፡ ብዙ ተሳትፎ የለውም፡፡ ጐልማሣው ይሻላል፡፡ ትልቅ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል፡፡ ቦርዱ በየ2 ዓመቱ ይመረጣል፡፡ ጐርፉ ይመጣል - እኛ በመከላከል ውጤት አምጥተናል፡፡ ዘንድሮ ዝናብ አለ - አዝመራው ይሰጣል!” አሉኝና በሳቸው በኩል ውይይቴን ጨረስኩ፡፡
ቀጥሎ፤ ኢኮኖሚስቱ የድሬዳዋ ልጅ አሸናፊ ደጀኔ የፕሮጄክት ሃላፊው እንዲህ አለኝ “ይህ ማህበር የጄክዶ ልጅ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ የፕሮጄክቱ ዓላማ ከጐርፉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በኢትጵያ ውስጥ በማህበረሰብ መልክ የመጀመሪያው ማህበረሰብ ነው፡፡ ፅንሰ ሃሳቡ ራሱ አዲስ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም፡፡ በማህበረሰብ ደረጃ በቅድመ -ማስጠንቀቂያ (Prewarining) መሥራት። 05ና02 ቀበሌዎች ላይ ነው የሚሠራው፡፡ ተፋሰሶች 2ቱ ስለሆኑ - ደቡብና ምዕራብ፡፡ 1ኛ) የማህበረሰቡን አቅም መገንባት። በግንዛቤ አደረጃጀት የመንደር ኮሚቴን ማጠንከር፡፡ ትሥሥር መፍጠር፡፡ የጐርፍ ቅነሳ መረብ (Net work) አለ፡፡ እዚህ ውስጥ ከገጠር ወደ ከተማ መረጃ መረብ ተዘርግቷል 2) የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የእርከን፣ የክትር፣ የመቀልበሻ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ጐርፍ የጐዳቸው 37 አባወራዎች ወደ እርሻቸው ይቀለበሳሉ፡፡ በቆሎ ማሽላ ይዘራሉ፡፡ ዋናው ግን የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ነው! ከምርት በዘለለ ጋራው ሲያበቅል ጐርፍ ይከላከላል፤ ሣርም እያጨዱ ለከብቶቻቸው ያበላሉ፡፡ በዘላቂነት እርሻም ይሠራሉ፡፡ አካባቢያቸውን ከጠበቁ በዘላቂነት ተጠቃሚ መሆናቸውን ለማየት ችለዋል፡፡ ዋናው የህብረተሰቡን ህይወት ከሥራው ጋር ማቆራኘት ነው። ከዛ ራሱ ይጠብቀዋል፡፡ ዘላቂ ይሆናል፡፡ ልማት ማለት ይሄው ነው! ሥራው ከብዙ ባለድርሻ ጋራ ስለምንሠራ ግንኙነት እንፈጥራለን፡፡ አገር አቀፍ ተቀባይነትና ዕውቅ ማግኘት ችለናል፡፡ መንግስት ይተባበረናል፡፡ የ3 ዓመት ፕሮጄክት በቀጣይ ቀርፀናል፡፡ 2014-2016 ዓ.ም ያለንን ዕቅድ ከጅምሩ እንዲያውቁት አድርገናል፡፡”
“እዚህ ውስጥ የጄክዶ ሚና ምንድን ነው” አልኩና ጠየኩት፡፡
“ጄክዶ ከሌሎች የሚለየው በጐርፉ አካባቢ ይሠራ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ የሠራቸው የልማት ሥራዎችም ያኔ አብረው ወደሙ - በጐርፉ፡፡ ስለዚህ ምን ይሁን ተባለ፡፡ ማህበረሰቡ ይህን ሃሳብ ይዞ ሲመጣ፤ ጄክዶ አስተባብረው፡፡ ጄክዶ ሀ) በቴክኒክ ለ) በፋይናንስ ሐ) በማቴሪያልም ደገፈ፡፡  ዕውቅና እስኪያገኝ ድረስ ሙሉ ነገሩን ሲደግፍ ነበር፡፡ አሁን ይሄን ፕሮጄክት ራሳችንን ችለን ነው የምንሠራው፡፡ በመጨረሻ ዕቅዱ የኔ ነው የሚል ዕምነት ይፈጠራል፡፡ ዘላቂነት ይሄ ነው! በዛ ያሉ ሴቶች የቤት ራስ - አገዝ፣ ቁጠባ፣ ህፃናትና አረጋውያን ላይ ነው የሚሠራው!
እንዲሣተፉ ወጣቶችን በችግኝ ተከላና አፈር ጥበቃ ያሳትፋል፡፡ ኢኮኖሚካሊ ሲጠነክር አደጋን የመቋቋም አቅምም ያገኛል!” አለኝ፡፡  
የድሬዳዋ ነገር
ስለ ድሬዳዋ ካወኳቸው ነገሮች በጣም የገረመኝ፤ “ድሬዳዋ ሲገቡባት የምታስደነግጥ፣ ሲወጡባት የምታስደነግጥ” የሚለው አነጋገር ነው፡፡
“እኔ የማውቀው ደሴን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳውቃት፤ “ደሴ፤ ሲገቡ አልቅሶ፣ ሲወጡ አልቅሶ’ ያሉኝን አባባል ነው”፤ አልኩት ስለ ድሬዳዋ ያጫወተኝን ወዳጄን አቤን። “ያኛው ለምንድነው? ደሴ ስትገባ ምድር ሰማዩ ይዞርብሃል፡፡ ላገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ትሆናለህ። በመንግሥት ለራ ተመድበህ ከሆነ፤ “እንዴት ሆኜ ነው እዚህ አገር የምዘልቀው?” ትላለህ፡፡ ቀስ በቀስ ካዳሚዋንም፤ አፍቃሪዋን ሴትም፤ የደሴን ጉራንጉርም፣ እንጉርጉሮና ዘፈንም፤ ስታውቅ “ፍቅር እዚህ ነው፣ ዘፈን እዚህ ነው፣ ህይወት እዚህ ነው” ትላለህ፡፡ የሥራ ጊዜህ አልቆ ወደ አዲስ አበባ ተመለስ ስትባል፤ “ዕንባ ዕንባ ይልሃል፡፡ እንዴት ነው ከደሴ እምለቅቀው?’ ትላለህ”፤ አልኩት፡፡
ወዳጄ፤ ስለድሬዳዋ የመለሰልኝ፤
“የድሬዳዋ ደሞ ለምን መሰለህ? ከተማው ዳርቻ የለውም፡፡ ድንገት ሃይ ስኩሉ ላይ ነው ዱብ እምትለው። ጠብ ጠብ የሚል የከተማ መቀነት፣ የገጠር ቤት አታይም፡፡ ሃይ ስኩሉ ከተማው እምብርት ላይ ነው፡፡ ድሬዳዋ ያለምንም መግቢያ የተፃፈ ድርሰት ናት!!  ከተማ መግባትክን ሳታቅ ከተማ ትገኛለህ፡፡ መጀመሪያ ገና ስትመጣ ትልልቁ ህንፃ ይቀበልሃል! ድንጋይ ማህል! በሩ ላይ፡፡ ምድር ባቡሩ መካከል!! ከዚያ ጀርባ - ጠፍ ነው! በቃ! ድሬዳዋ ድንገት ገብተህ ድንገት የምትወጣባት ከተማ ናት” አለኝ፡፡
ውነቱን እኮ ነው! “እንደሌላ ከተማ ዳር ዳሩ አያጫውትህም?!” አልኩት፡፡
“እግዜር ይስጥሀ አቦ! እቺ ናት ከገጣሚ የምትፈለገው! አያዋዛም! ድንገት እንደብራ መብረቅ ዱብ ይልብሃል!”
“ልክ እንደጐርፍ?” አልኩት ፍርጥም ብዬ፡፡
“አሁን ወደ ጉዳያችን ገባህ! እኔ ደራሲ እማደንቀው ለዚህኮ ነው!...
አሁን እንግዲህ ‘የድሬዳዋ ኮሙኒቲ አክሽን የበጐ አድራጐት ማህበር’ን ላስተዋውቅህ ነው” አለኝና ወደ ማህበሩ ጽህፈት ቤት ወሰደኝ፡፡
ሰብሳቢውን አገኘናቸው፡፡ አጭር ጠይም፡፡ ጠና ያሉ፡፡ ድምፃቸው ግርማ ሞገስ ያለው፤ አንደበተ ርቱዕ ሰው ናቸው፡፡ ድምፃቸው ከአቅማቸው በላይ ጠንካራ ነው፡፡ አቤ አስተዋወቀኝና፤ “በክልል ውስጥ የሌሉበት ኮሚቴ ትንሽ ነው… በሚመቻችሁ መልኩ ተነጋገሩ ብትፈልጉ ዙሩ፡፡
“ድሬዳዋ ኮሙኒቲ አክሽን በጐ አድራጐት ማህበርን” (DDCAን) ለምን ፎርም ማረግ አስፈለገ ከጀርባ ታሪኩ ጀምሩ” ብሎ አቤ ትቶን ሄደ፡፡
“እሱን ለእኔ ተወው” አልኩትና ወደ አቶ ብርሃነ ዞሬ፤ “እህስ እጅዎ ከምን?” ብዬ ጀመርኩ፡፡
(የድሬዳዋ ጉዞዬ ማስታወሻ ይቀጥላል)

Published in ህብረተሰብ

አራቱ ትልልቅ የነዳጅ ኩባንያዎች ይፎካከሩባቸው ነበር
የበርካታ ቤተ - ክርስቲያናት ሊቀ ካህን ሆነው አገልግለዋል
በ84 ዓመት እድሜያቸው ያለመነፅር በፍጥነት ያነባሉ
63ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን በድምቀት አክብረዋል

አለቃ ገ/እግዚአብሔር ገብረየሱስ ይባላሉ፡፡ በአድዋ አውራጃ ማሪያም ሸዊት በምትባል ቦታ በ1922 ዓ.ም እንደተወለዱ ይናገራሉ፡፡ የ84 አመቱ አዛውንት በትውልድ አካባቢያቸው የቤተ - ክህነት ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ፣ በ1943 ዓ.ም ከአቡነ ይስሃቅ ሊቀ ካህን በሚል ማዕረግ ተሰይመው ለአመታት አገልግለዋል፡፡
ዘመናዊ ትምህርታቸውን እስከ ስድስተኛ ክፍል የተማሩት አለቃ ገ/እግዚአብሔር፤ እስከ 1949 ዓ.ም በማሪያም ሸዊት ገዳምና በአባ ገሪማ ገዳም ውስጥ በሚገኙ ቤተክርስቲያናት በካህንነት ያገለገሉ ሲሆን በ1951 ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ፤ የዘመዳቸው ድርጅት በሆነው አምቦ ጠበል ፋብሪካ፣ በራስ ሆቴል እና በብሔራዊ ባንክ ተቀጥረው ሲሰሩ ቆይተው፣ ትንሽ ሱቅ በመክፈት ነዳጅ እና የሞተር ዘይቶች መቸርቸር ይጀምራሉ፡፡  ይህንን ስራቸውን በጥረት በማሳደግ ከሞቢል፣ ከአጂፕ፣ ከሼልና ቶታል ኩባንያዎች ነዳጅ በቅናሽ በመውሰድ የለየላቸው ነዳጅ አከፋፋይ በመሆን በቀን 30ሺህ ሊትር እስከመሸጥና ከሞቢል ኩባንያ ነዳጅ ማደያ እስከ መሸለም በቅተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ አዲሱ ገበያ በሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው ተገኝታ ስለ ንግድ ስራቸው፣ ስለ ትዳር ህይወታቸው፣ ስለ ቀድሞው እና ስለአሁኑ አጠቃላይ የህይወት ሁኔታና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከአዛውንቱ ጋር ቀጣዩን አድርጋለች፡፡


ትውልድና እድገትዎ የት ነው?
ትግራይ ውስጥ አድዋ አውራጃ፣ ማሪያም ሸዊት በሚባል ቦታ ነው ተወልጄ ያደግሁት፡፡ ወደዚህ ምድር የመጣሁት በ1922 ዓ.ም ነው፡፡
ከትውልድ ስፍራዎ እንዴት ወደ አዲስ አበባ መጡ? መቼስ ነው የመጡት?
ወደዚህ የመጣሁት በ1951 ዓ.ም ነው፡፡ አመጣጤ ገጠርና ጠባብ ከተማ ውስጥ ከመኖር ሰፊ በሆነው አዲስ አበባ ብኖር ይሻለኛል ብዬ ነው፡፡
በትውልድ አካባቢዎ የቀለም ትምህርት ቀስመው ነበር እንዴ?
በአብዛኛው በደንብ የተማርኩት የቤተ - ክህነት ትምህርት ነው፡፡ ነገር ግን ዘመናዊ ትምህርትም እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምሬ ነበር፡፡
ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ማን ተቀበለዎት? ዘመዶች ነበሩዎት?
የተፈሪ ሻረው እናት ዘመዴ ነበረች፤ እርሷ ናት የተቀበለችኝ፡፡
ተፈሪ ሻረው ማን ናቸው?
የአምቦ ጠበል ፋብሪካ ባለቤት ነበር ተፈሪ ሻረው፤ እናቱ የቅርብ ዘመዴ ናት፡፡
ብቻዎትን ነው ወደ አዲስ አበባ የመጡት?
ታናሽ እህቴንም ይዣት ነው የመጣሁት፡፡ ለምን ብትይ… ገና ትንሽ ሆና ሊድሯት ነበር፡፡ ልጅቱን ስጡን ጥንድ በሬ እንሰጣችኋለን እያሉ ሲነጋገሩ ሰምቼ፣ አሁን ከምታገባ በጉልበቷ ሰርታ ትበላለች ብዬ ይዣት መጣሁ፡፡ ሂሩት ገ/የሱስ ትባለለች፡፡ ያን ጊዜ አውቶቡስ አምጥቶ ጊዮርጊስ አካባቢ ጣለን፡፡ አሜሪካ ጊቢ አንድ እህት ነበረችኝ፡፡ መጀመሪያ እሷ ጋር አረፍኩ፡፡ ከዚያ በኋላ አድዋ ማሪያም ሸዊት የተወለዱ የአገር ሰዎች ነበሩ፡፡ “አለቃ መጥተዋል ተቀበሏቸው” ብለው መኝታው፣ ጮማው ተይው… ጥሩ አቀባበል ተደረገልኝ እልሻለሁ፤ እነዚህ ሰዎች ለመሬት ሙግት ከአዲስ አበባ ወደ አድዋ ሲመጡ እኔም ጥሩ አቀባበልና መስተንግዶ አድርጌላቸው ነበር፡፡ የተፈሪ ሻረው እናት ወ/ሮ አዛለችም ጥሩ አቀባበል አድርጋልኛለች፡፡
እንግድነትዎን ጨርሰው ምን ስራ ላይ ተሰማሩ?
በወቅቱ የአምቦ ጠበል ባለቤት አቶ ተፈሪ ወደ ውጭ ይሄድ ነበር እና ሌላ ስምንት ሰው ጨምሬ አምቦ በመሄድ እዛው ፋብሪካው ውስጥ ካቦ ሆኜ መስራት ጀመርኩ፡፡
በስንት ብር ደሞዝ ተቀጠሩ?
በሳምንት ስምንት ብር፣ በወር 40 ብር አካባቢ ነው፡፡ ያኔ ብዙ ብር ነው ለእኔ፡፡ እዛ እስከ 1954 ዓ.ም ከሰራሁ በኋላ ጥየው መጣሁ፡፡
አዲስ አበባ ከመምጣትዎ በፊት ትዳርና ልጆች እንደነበሩዎት ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ይንገሩኝ …
በ1942 ነው የአሁኗን ባለቤቴን ሙሉ ግደይን ያገባሁት፡፡ እዚህ ከመምጣቴ በፊት ሁለት ልጆቼን እዛው ማሪያም ሸዊት ነው የወለድኩት፡፡ እዚህ በመጣሁ በሁለት አመቴ ሚስቴንና ልጆቼን አባቴ ይዘውልኝ መጡ፡፡ አምቦ ሆኜ ተቀበልኳት፡፡ ከዚያ… በኋላ ስድስት ልጆች ጨመርን፡፡ አንዱ ሲሞት ሰባቱ አሉ፡፡ የልጅ ልጅም፣ የልጅ ልጅ ልጅም አሳይተውኛል፤ ቅድመ አያት ሆኛለሁ፡፡
ስንት የልጅ ልጆችና የልጅ ልጅ ልጆች አሉዎት?
ሀያ የልጅ ልጆች፣ ሁለት የልጅ ልጅ ልጆች አሉኝ፡፡
ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ምን አይነት ስራ ጀመሩ?
ከአምቦ እንደመጣሁ ራስ ሆቴል ውስጥ ተቀጠርኩኝ፡፡ መጀመሪያ የሰራሁት አራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በካፍቴሪያ ውስጥ ነው፡፡ በወቅቱ ዩኒቨርስቲው በታህሳስ ግርግር ተዘግቶ ነበር፡፡ ራስ ሆቴል የዩኒቨርስቲውን ካፍቴሪያ ኮንትራት ይዞ ይሰራበት ስለነበር እዛ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ከታህሳስ ግርግር በኋላ ጃንሆይ ቤተ-መንግስታቸውን ለዩኒቨርስቲነት ሰጥቻለሁ ብለው ቃል ሲገቡ (የአሁኑን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማለት ነው) ወደ ዩኒቨርስቲው ተዛወርኩና ሰራሁ። ይህ በ1956 ነው። በ1957 ደግሞ ብሄራዊ ባንክ ተቀጠርኩ፡፡ ባንክ እየሰራሁ ነው በበርሜል ነዳጅ መሸጥ የጀመርኩት፡፡
ነዳጅ መሸጡን እንዴት አሰቡት?
እንዴ! ስራ መፍጠር አለብኛ ምን ማለትሽ ነው? (ኮስተር አሉ) ተቀጥሮ በመንግስት ቤት ብቻ መስራት እኮ ፅድቅ አይደለም! ጠዋት ወደ ባንክ ከመግባቴ በፊት ነዳጅ የሚወስድ ነጋዴ ስፈላልግ አረፍዳለሁ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልኩ ከአራቱም ኩባንያዎች ማለትም ከቶታል፣ ከአጂፕ፣ ከሼልና ከሞቢል ነዳጅ በቅናሽ እየወሰድኩ እሸጥ ጀመር፡፡
እንዴት ከአራቱም እየወሰዱ ያከፋፍላሉ? ኩባንያዎቹ ተፎካካሪዎች አይደሉም እንዴ? አሁን ጊዮርጊስ ቢራ የሚያከፋፍሉ ቢሆን ሌሎች ቢራዎችን ዞር ብለው እንዲያዩ አይፈቀድም?
እኔ በወቅቱ ያለ ምንም አድልዎ የአራቱንም ኩባንያዎች በበርሜል እየወሰድኩ በየክፍለ ሀገሩ አከፋፍል ነበር፡፡ እርግጥ የእኛን በደንብ ውሰድ፣ የእኛን በብዛት ሽጥ እያሉ ይጫረቱ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ እኔን ለማበረታታት ነዳጁ ላይ ቅናሽ አድርገውልኝ ነበር፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልኩ በስራው ገፋሁበት፡፡
ሞቢል የካ አካባቢ ማደያ ሸልሞዎት ነበር፡፡ እንዴት ሊሸልምዎት እንደቻለ ቢነግሩኝ?
ሞቢል የሸለመኝ አንደኛ በአንድ ቀን 150 በርሜል (30 ሺህ ሊትር) ነዳጅ በመሸጤ ነው፡፡ ሁለትም እነ አጂፕ ሼልና ቶታል ጀነራል ማናጀሮቹ እየጠሩኝ ከእኛ ግዛ፣ ከእኛ ጋ ስራ ማለት ሲያበዙ፣ ቀድሞ እኔን ለመያዝ ነው ሞቢል ማደያውን የሸለመኝ፡፡ ረጅም ጊዜ ሰርቼበታለሁ፡፡
አሁንም ማደያው እየሰራ ነው ወይስ …?
ለራሳቸው መልሼላቸዋለሁ፡፡
በምን ምክንያት?
እዛው ማደያው ላይ ስሰራ የመኪና አደጋ ደርሶብኝ እግሬ ተጐዳ (አደጋው ያደረሰውን ረጅም ጠባሳ ቱታቸውን ሰብስበው አሳዩኝ፤ የከፋ አደጋ እንደነበር ይጠቁማል) በአደጋው ለአንድ አመት ያህል ምኒሊክ ሆስፒታል ተኛሁ፡፡ (ከ1963-64 ዓ.ም) መሆኑ ነው፡፡ በወቅቱ ወንድሜና ዘመዶቼ እንዲሰሩ ሃላፊነት ሰጥቻቸው ነበረ፡፡ ሆኖም በአግባቡ ሊሰሩ ስላልቻሉ ለኩባንያው መለስኩለት። ነገር ግን መጀመሪያ የከፈትኩት የሞተር ዘይት መቸርቸሪያ ሱቅ ስለነበረ እሱ ስራውን ቀጠለ። የሞተር ዘይት ብቻ ሳይሆን በበርሜልም ነዳጅ አከፋፍል ነበር፡፡ ማደያውን ከመለስኩ በኋላ ማለት ነው፡፡ መጀመሪያም የጀመርኩት በሱቅ ነበር፡፡
ነዳጅ በወቅቱ በሊትር ስንት ነበረ?
ይታይሽ… ከጅቡቲ የታሸገው በርሜል ነዳጅ በ15 ብር ነው የሚመጣልን፡፡ በ15 ብር ተረክበን ነው የምንሸጠው (በጣም እየሳቁ) በሊትር 15 ሳንቲም ይሁን አስር ሳንቲም… ብቻ ከዚህ አይበልጥም ነበር፡፡
እርስዎ ነዳጅ መሸጥ ሲያቆሙ ነዳጅ በሊትር ስንት ነበር? እስኪ ያስታውሱ?
ውይ እሱን አላስታውስም… ብቻ እኔ ሳቆም በሊትር አንድ ብር የገባ አይመስለኝም፡፡
እስኪ ስለ ትዳርዎ እናውራ፡፡ አሁን ወ/ሮ ሙሉ ግዴይ የት አሉ? እድሜያቸውስ ስንት ሆነ?
አለች ጓዳ ውስጥ ስራ ላይ ናት፤ እድሜዋ ከእኔ በአምስት አመት ያንሳል፡፡ ከተጋበን 63 አመታችን ነው፡፡ በቅርቡ 63ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላችንን ልጆቻችን ድል ባለ ድግስ አክብረውልናል፡፡ ተዓምር የሆነ ድግስ ነው፡፡ ልጄ ቢኖር በፊልም የተቀዳውን ያሳይሽ ነበር፡፡
ነዳጅና የሞተር ዘይት ያከፋፍሉበት የነበረው ሱቅ አሁን ምን ሆነ?
አለ ይሰራል፡፡ ነገር ግን ነዳጅ ሳይሆን የህትመት ወረቀት አስመጪ ድርጅት ነው የሆነው፡፡ ልጄ ዘካሪያስ ውክልና ወስዶ እየሰራበት ነው፤ ያው ከንግዱ አልወጣሁም፡፡
በትውልድ አካባቢዎ ለካህንነት ለተሾሙበት ማሪያም ሸዊት እርዳታ እንዳደረጉም ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ይንገሩኝ?
ለማሪያም ሸዊት መብራት አብርቼለታለሁ፡፡
አብርቼላታለሁ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
መብራት ከመብራት ሃይል ጠልፌ በገንዘቤ አስገብቼ፣ የመብራት ተጠቃሚ አድርጌያለሁ። ከቤተ ክርስቲያኑ እየወሰደ የአካባቢውም ሰው መብራት ይጠቀማል፡፡ በተጨማሪም ለቤተ - ክርስቲያኗ አራት ወፍጮ ተክዬ በገቢው እየተጠቀመች ትገኛለች፡፡ ይህን ያደረግሁበት ከደርግ ውድቀት በኋላ ነው፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ አድዋ የሄዱት መቼ ነው?
እስከ ቅርብ ጊዜ እሄድ ነበር፡፡ እስከ 2000 ዓ.ም። ከዚያ በኋላ አልሄድኩም፤ ትንሽ እያመመኝ ነው፤ እዛ መኖሪያ ትልቅ ቤት ሰርቻለሁ፡፡ ልጄ ዘካሪያስም ቤት አለው፤ ማሪያም ሸዊት ከአድዋ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ነው የሚርቀው፡፡ ይሄ ገዳም ይገርምሻል በ1945 ተቃጥሎ ነበር፤ እንደገና ነው የተሰራው። ደጃች ሀጐስ ተሰማ የተባሉ ዘመዳችን ሄደው ፕላን አንስተው ከመጡ በኋላ፣ ለጃንሆይ ነግረው ነው መልሶ የተሰራው፡፡ በዚህ የቤተክርስቲያን ስራ ውስጥ አባቴም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ እስካሁንም ለቤተክርስቲያኗ ፍቅር አለኝ፡፡ አሁንም ለህዳር ማሪያም ለአመቱ ቢኒያምን (ልጃቸው ነው) ካባና ፅናፅል ግዛ ብዬዋለሁ፡፡ አሁን ድምፅ ማጉያም ያስፈልጋል፤ እሱንም ልጄን ግዛ ብዬዋለሁ፡፡
አሁንስ ወደ አድዋ የመሄድ ፍላጐት አለዎት?
በደንብ ፍላጐት አለኝ፤ ትንሽ ይሻለኝና እሄዳለሁ። የፈጣሪ ፈቃድ ይሁን… ትንሽ እግሬ ያስቸግረኛል፡፡
አባባ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ በትምህርትዎ እንዴት አልገፋም?
ከዚያ በኋላማ ልጆች መጡ፤ እነሱን ወደማስተማሩ ነው የሄድኩት፡፡ ምክንያቱም ከአድዋ ባለቤቴ ሁለት ልጆቼን ይዛ መጣች፡፡ እዚህም ተጨማሪ ልጆች አፈራን፡፡ ከዚያ “ትምህርት ለምርት” በሚል መርሆ ለልጆች ቅድሚያ ሰጥተን ማስተማርና ማሳደግ ስንጀምር የእኔን ትምህርት ዘነጋሁት፡፡
ባንክ ቤት የሰሩት በስድስተኛ ክፍል የትምህርት ደረጃዎት ነው?
አዎ በዛው ነው፤ ግን በደንብ እውቀት ነበረኝ። በወቅቱ ትምህርቱም በደንብ ነበር የሚሰጠው፡፡
አሁን ነዳጅ በሊትር ስንት እንደገባ ያውቃሉ?
ውይ አሁንማ በጣም በጣም ውድ ሆኗል። መቼም ጊዜ ሲለወጥ ሁሉም ይለወጣልና ምን ይደረግ፡፡
እስቲ የቀድሞውንና የአሁኑን ትውልድ ያነፃጽሩልኝ?
አሁን ጊዜው ወርቅ ነው፡፡ ወጣቱም ጐበዝ ሆኗል፡፡ ቴክኖሎጂው ሁሉ ድካም እየቀነሰ ነው፡፡ አሁን ድሃ ሃብታም የለም፤ ሁሉም መማር ይችላል። ዋናው የራስ ጥረት ነው እንጂ ለመስራትም ለመማርም እድሉ አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቀጣፊ ቦታ የለውም፡፡
እንደሚባለው ቀጣፊ፣ ሙሰኛ፣ አጭበርባሪው የበዛው አሁን ነው፡፡ የድሮ ሰዎች ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ናቸው ይባላል፡፡ እውነት ነው?
እርግጥ ሙሰኛ ሌባ ሙሉ በሙሉ የለም ማለት አይደለም፡፡ ይሄው እየተጋለጡ ወህኒ እየወረዱ ነው። ሌባ ሁሌ አይቀናውም፤ የሚሰርቅ ሁሉ እየተጋለጠ ነው፡፡ አሁን ጊዜው ትውልዱ በእኔ እምነት ደስ የሚልና የሰለጠነ፣ የሚሰራና የሚማር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች አገራቸውን መውደድ አለባቸው፡፡ በአገራቸው መስራት አለባቸው፣ ስደት መጥፎ ነው፤ ከስደት መቆጠብ አለባቸው፡፡ አሁን እዛ የማይረባ አረብ አገር ሄደው ለሞትና ለውርደት ነው የተዳረጉት፡፡
ግን እኮ ኢትዮጵያውያን የሚሰደዱት ወደው ሳይሆን ስራ በማጣት ነው እየተባለ ነው?
ነገርኩሽ! እኔ እኮ ስራ ፈጠርኩ፤ ባንክ ቤት እየሰራሁ፣ ጠዋት 12 ሰዓት ወጥቼ በርሜል ይዘው ነዳጅ ለመውሰድ የሚመጡ ነጋዴዎች የሚያድሩበትን ቦታ በጐን እፈልግ ነበር፡፡ ከባንክ የማገኘው ደሞዜ ይበቃኛል ብዬ እጄን አጣጥፌ አልቀመጥኩም። ምንም ቢሆን አገር ይሻላል፡፡ ስራ መፍጠር፣ የተገኘውን መስራት የግድ ነው፡፡ እሰው አገር ሄዶ ከመሞትና ከመዋረድ ራስን መጠበቅ አስፈላጊ ነው። ዋናው ስራ ሳይንቁ ሰርቶ መለወጥ ነው፡፡ ፍላጐቱ ካለ ስራ አይጠፋም፡፡ ስራ አጣሁ ብሎ ራስን ወደ ሞት አገር ማሰደድ እብደት ነው እላለሁ፡፡
አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ መንፈሳዊ ህይወትዎ ምን ይመስላል?
እዚህም ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ነበርኩ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ መፅሐፍ ቅዱስ ሁሉ ሸልሞኛል፤ ከዚያ አልጠፋም ነበር፡፡ ያው እድገቴም ቤተ - ክህነት ስለሆነ ቤተክርስቲያን እወዳለሁ፡፡ መንፈሳዊ ህይወቴ ጥብቅ ነው፡፡ የቤተ - ክርስቲያን በርካታ መጽሐፍት አሉኝ። ይሄ የምታይው ዳዊት ነው (ወደ የቤታቸው ስንገባ ይደግሙት የነበረውን ቀይ ሽፋን ያለው መዝሙረ ዳዊት እያሳዩኝ) ስንት መጽሐፍ አለኝ መሰለሽ
አሁን እድሜዎት 84 ዓመት ደርሷል፡፡ መዝሙረ ዳዊት ሲያነቡ ያገኘሁዎት ያለመነጽር ነው፡፡ አይንዎት እንዴት ነው?
ኦ…ኦ…አይኔ ግሩም ነው፤ በደንብ አያለሁ፣ በደንብ አነባለሁ፤ ጆሮዬ በደንብ ይሰማል፡፡ ምንም ችግር የለብኝም፡፡
አይኔ መነጽር አጥልቆ አያውቅም። ወደፊትም አልፈልግም፡፡ እስቲ ላንብብልሽ፡፡ (ግዕዙ ባይገባኝም እርሳቸው ግን በፍጥነት አንበለበሉት)
አሁን ኑሮ እንዴት ነው? ልጆችዎት በደንብ ይንከባከቡዎታል?
በጣም በጣም ልጆቼ ይወዱኛል፡፡ ወልደሽ ልጅ ሲባረክልሽ ጥሩ ነው፡፡ ልጆቼ በደንብ ይዘውኛል። እኔ እንኳን አድዋ እቀመጣለሁ ብዬ ነበር፤ ግን እግዚአብሔር ፈቅዶ እዚሁ እየፀለይኩ ነው፡፡ ሸዋ እንደሆነ ብሩክ አገር ነው እኔም ባለቤቴ ሙሉ ግደይም ተወደን ተከብረን በደንብ እየኖርን ነው፡፡ አነባለሁ እፀልያለሁ፡፡ ይገርምሻል… ብራና መጽሐፍ ሁሉ አለኝ… ላሳይሽ (ከዘራቸውን ድጋፍ አድርገው ከሳሎን ወጥተው በርካታ መጽሐፍ ይዘው መጡ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራና መጽሐፍ ማየቴና መንካቴ ነው)
ከየት አመጡት? ይህን አይነት ብራና መጽሐፍ አሁን በግለሰቦች እጅ አይገኝም ብዬ ነው?
ልክ ነሽ አሁን አሁን እንኳን በግለሰብ እጅ በቤተ - ክህነትና በገዳማት ብዙ ያለ አይመስለኝም። ዱሮ ጠጅ ለመጠጣት፣ ጮማ ለመቁረጥ ገዳም ሰፈር እንመጣ ነበር፡፡ ታዲያ ያኔ አሁን ሴትዮዋ ሞተዋል፡፡ ባላቸው ዳኛ ነበሩ፡፡ “ይህን መጽሐፍ ቱሪስት ከሚወስደው እርሶ ይግዙት ቅርስ ነው” ብለው በ15 ብር ሸጡልኝ። ይሄው ቅርስ ሆኖ እኔም አንብቤው ተቀምጧል፡፡ ሌላም በርካታ መጽሐፍት አሉኝ፡፡ (የብራና መጽሐፉን አሰራርና ከምን እንደተሰራ እያገላበጡ አሳዩኝ፤ ከመጽሐፉ አንድ ምዕራፍ ያህል በፍጥነት አነበቡልኝ)
አሁን ፎቶ ላነሳዎት ነው ይዘጋጁ…
እንደዚህ የቤት ልብስ ለብሼማ አይሆንም። ባይሆን ትንሽ ታገሺኝ፤ ከወገቤ በላይ ሌላ ልብስ ልልበስ፡፡ ጋዜጣሽን እንዳላበለሻብሽ (አሁንም በከዘራቸው ድጋፍ ወደ መኝታ ቤት ገብተው ሽሮ መልክ ያለው ንፁህ ሸሚዝና ግራጫ ቀለም ያለው ኮት ደርበው ተመለሱ) አሁን እንግዲህ እንደፈለግሽ አንሺኝ፡፡
አበባ ገ/እግዚአብሔር፤ በጣም እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ ስለ ትብብርዎ አመሰግናለሁ…
እኔ ላመስግን እንጂ… እኔን ፈልገሽ ቁም ነገር ለመስማት የመጣሽው አንቺ ተባረኪ የኔ ልጅ፤ አመሰናግለሁ፡፡

Published in ህብረተሰብ

‘በርካታ’ ስንት ነው?

ተፈጥሮ በፊሊፒንስ ላይ ፊቷን አዞረችባት፡፡
ድንገት ከተፍ ያለውና ሱፐር ታይፎን ሃያን የሚል ስም ያወጡለት አሰቃቂ አደጋ አገሪቱን እንዳልነበረች አደረገ፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለርሃብ፣ ለእርዛትና ለአስከፊ መከራ ዳረገ፡፡
ፊሊፒንሳውያን ሸሽተው ሊያመልጡት ያልቻሉት የጥፋት ማዕበል ሳይታሰብ ከተፍ ብሎ  አያደርጉ አደረገና ወደመጣበት ተመለሰ፡፡ አስከሬን በየአቅጣጫው የወደቀባት፣ ይልሱ ይቀምሱት… ይደርቡ ይለብሱት የሌላቸው የጥፋቱ ትራፊዎች አንዳች መላ ፍለጋ አይናቸውን ወደተቀረው አለም አሻግረው የወረወሩባት፣ እንዳታገግም ሆና የተመታች፣ ፍርስራሽ ፊሊፒንስን ትቶ ሄደ፡፡
ከአሰቃቂው ሱፐር ታይፎን ሃያን በተአምር መትረፍ ዕድለኛነትን ይጠይቃል፡፡ ሻለቃ ኢልመር ሶሪያም ከማዕበሉ ካመለጡ ዕድለኛ ፊሊፒንሳውያን አንዱ ነበር፡፡ ነበር ነው ታዲያ!...
የአገሪቱ ብሄራዊ ፖሊስ አባል የሆነው ሻለቃ ኢልመር ሶሪያ፣ ፊሊፒንስን አውድሞ ያለፈው የጥፋት ማዕበል እንደገና ተመልሶ ያጠቃው፣ አሳዛኝ ሰለባ መሆኑን ሮይተርስ ባለፈው ሰሞን ዘግቧል። ዘገባው እንደሚለው ሻለቃ ኢልመርን የዘገየውን የአደጋው የመከራ ጽዋ ያስጎነጨው የአፍ ወለምታ ነው፡፡
የአለማችን ሰሞነኛ መነጋገሪያ የሆነውን አደጋ በተመለከተ መረጃ የፈለጉ ጋዜጠኞች ወደ ሻለቃው ቢሮ ብቅ ይላሉ፡፡ እሱም ስለአደጋው አስከፊነትና ስላደረሰው ሁለንተናዊ ጥፋት መረጃ ሰጥቶ ነበር። “ሱፐር ታይፎን ሃያን ከ10ሺህ በላይ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል” በማለት፡፡ ጋዜጠኞቹ ዘገባውን ሰሩ፡፡ ዘገባውን የተመለከቱ ባለስልጣናት በቁጣ ነደው ፊታቸውን ወደ ሻለቃው አዞሩ፡፡
“ከአለቆችህ ጋር ተማክረህ መረጃ እንደመስጠት፣ የምን አፍህ እንዳመጣልህ መዘባረቅ ነው!?... ያልሞተ ሰው ሞቷል እያልክ ክፉ ማውራት ምን እሚሉት ኩሸት ነው?!” አሉት አለቃው፡፡
ሻለቃ ኢልመር ሶሪያ ለአለቃው መልስ ይስጣቸው፣ አይስጣቸው ዘገባው ያለው ነገር ባይኖርም፣ ‘የሟቾችን ቁጥር የማጋነን ወንጀል ፈጽሟልና መቀጣት አለበት’ ተብሎ መወሰኑንና፣ በዚህ የጭንቅ ጊዜ ከስራ ገበታው መባረሩን ነው ሮይተርስ ለአለም ያሰማው፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንትም ይሄን ተከትሎ፣ “የሞቱብን ዜጎች 2500 ያህል ብቻ ናቸው። ይሄ አስር ሺህ ምናምን የሚሉት ነገር ፍጹም የተጋነነ ቅጥፈት ነው!” በማለት ለሲኤንኤን ማስተባበላቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ተጋኗል የተባለው የአደጋ መረጃው፣ ምስኪኑን ፖሊስ ለሌላ አደጋ ዳርጎታል፡፡
አዎ! ጥሩ አድርጎ መገመት አለመቻል፣ ምስኪኑን ሻለቃ ያልገመተው አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡ እርግጥ ከአደጋው ስፋትና ከፍለጋው አለመቋጨት አንጻር የሞተውን ሰው ትክክለኛ ቁጥር መገመት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ይህን መሰሉ ሰፊ ክስተት ተጠቂ ያደረገውን ሰው ቁጥር በአግባቡ መገመት አለመቻል፣ የሻለቃው ችግር ብቻ አይደለም፡፡ የብዙዎች በተለይ ደግሞ የጋዜጠኞች እንጂ፡፡
*   *   *                
“ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራትን አከናውነን፣ በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበናል”  - መንግስት
“ገዢው ፓርቲ ለበርካታ ዜጎች ስደት፣ ስቃይና እንግልት ተጠያቂ ነው”   - ተቃዋሚዎች
በርካታ ‘በርካታዎች’ን በየመገናኛ ብዙሃኑ ለበርካታ ጊዜያት የሰማችሁ በርካቶች እንደምትሆኑ ይሰማኛል፡፡ “ለመሆኑ በርካታ ስንት ነው?” ብላችሁ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ?
በርካታ፣ አያሌ፣ ዘርፈ ብዙ፣ የተለያዩ፣ መጠነ ሰፊ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥቅል ቃላት በየዜናው ውስጥ በተደጋጋሚ (ይሄው ቃል ራሱ) ሲነገሩ ይደመጣሉ። እንዲህ ያሉት ቃላት ብዛትን የሚገልጹ መሆናቸው ባይካድም እቅጩን አይናገሩም፡፡ መሰል ቃላት በዜና ውስጥ ተደጋግመው የመሰማታቸው ሰበብ፣ አንድም ከባለ ዜናው ሁለትም ከጋዜጠኛው ይመነጫል፡፡
‘ልማቱን ለማፋጠን በርካታ ተግባራትን አከናውነን፣ በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበናል’ በሚል የሆነን ሚኒስቴር መ/ቤት ሪፖርት የሚያትት አንድ ዜና ውስጥ ሁለት እውነቶች አሉ (ታመኑም አልታመኑም)፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ውጤቶችንም አስመዝግቧል፡፡ ጥያቄው ምን ምን ተግባራት ተከናውነው፣ ምን ምን ውጤቶች ተመዘገቡ ነው፡፡ መሰል ጥያቄዎችን አደባብሶ ማለፊያ የተለመደች መላ ናት - ‘በርካታ’!!
ይህቺ ቃል መግለጫ በሚሰጡ ባለስልጣናትና በሚመለከታቸው ሃላፊዎች ብቻ ሳይሆን በጋዜጠኞችም የተለመደች ናት፡፡ እርግጥ እንዲህ ያለውን አማራጭ ለመጠቀም አስገዳጅ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ፡፡ ጋዜጠኞች መረጃዎችን በቁጥር ለማስቀመጥና ይሄን ያህል ብለው እቅጩን ለመናገር የማይችሉባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለት አማራጮች ይጠቀማሉ፡፡ አንደኛው ግምታዊ መረጃ መስጠት ሲሆን፣ ሌላው ‘በርካታ’ በሚል ቃል ነገርየውን አደባብሶ ማለፍ ነው፡፡
ችግሩ ግምታዊ መረጃ እንደየጋዜጠኛውና እንደየሚዲያ ተቋሙ አቋም የሚለያይ መሆኑ ነው፡፡ “አንድነት” ፓርቲ ከወራት በፊት የጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ በተመለከተ በተሰሩ ዘገባዎች ላይ የተፈጠረውን ልዩነት የምንረሳው አይደለም፡፡ ይሄኛው ‘ይሄን ያህል ህዝብ ተገኝቷል’ ሲል፣ ያኛው ‘የለም ይሄን ያህል ነው’ ብሎ ዘግቧል፡፡ የተሰላፊው ህዝብ ቁጥር መለያየቱም አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡
መሰል ልዩነቶች በአብዛኛው ከሁለት ወገኖች እየቅል የሆነ ፖለቲካዊ ፍላጎት ሊመነጩ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ የአለማቀፍ ጋዜጠኞች ኔትዎርክ ድረገጽ ማኔጂንግ ኤዲተር ጀሲካ ዌስ ግን፣ ችግሩ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ሞያዊም ነው ትላለች፡፡ በጉዳዩ ላይ ያስነበበችው ጽሁፍ፣ እርግጥም በሰልፈኛ ቁጥር የሚወዛገቡት አንድነትና ኢህአዴግ ብቻ እንዳልሆኑ ያሳያል፡፡ ቀጥር አሳነስክ፣ ቁጥር አበዛህ ተብለው የሚታሙም የኛ ጋዜጠኞች ብቻ እንዳልሆኑም ይጠቁማል፡፡ ጉዳዩ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሞያም ጭምር ነው ትላለች - ጄሲካ፡፡
ጀሲካ ዌስ እንደምትለው፣ ብዙ ሰዎችን የሚያሳትፉ ሁነቶችን በተመለከተ በሚሰሩ ዘገባዎች ላይ የሰዎችን ቁጥር መገመት፣ በአለማቀፍ ደረጃ የሚታይ የጋዜጠኞች ፈተና ነው፡፡ ጄሲካ፤ ግብጻውያን የመሃመድ ሙርሲን መንግስት በመቃወም በቅርቡ አደባባይ ወጥተው ያደረጉትን ሰልፍ በዋቢነት ትጠቅሳለች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ በወቅቱ አንዳንድ ጋዜጠኞች ይህንን የተቃውሞ ሰልፍ “በአለማችን ትልቁ የተቃውሞ ሰልፍ” በማለት ጠቅሰውታል። እነዚህ ጋዜጠኞች በሰልፉ የተሳተፉትን ሰዎች ብዛት 30 ሚሊዮን አድርሰውታል፡፡ ሌሎች ጋዜጠኞች በአንጻሩ ቁጥሩን ወደ 14 ሚሊዮን ዝቅ አድርገውታል። ይህ ልዩነት ሊፈጠር የቻለው፣ የህዝቡን ቁጥር ለመገመት የሚያስችል መለኪያ ባለመኖሩ ነው ባይ ናት ጀሲካ።
በተለይ ከተቃውሞ ሰልፎች ጋር በተያያዙ ዘገባዎች የተሳታፊዎች ብዛት ከሚዲያ ሚዲያ እጅጉን የተራራቀ እንደሚሆን የጠቀሰችው ጄሲካ፣ ይህም የሚሆነው የተለያየ አቋም ላይ ያላቸው ፓርቲዎች ቁጥሩን ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ለማዋል በመፈለጋቸው ነው ትላለች፡፡
“ምን ያህል ሰው ተሳተፈ?” ለሚለው ጥያቄ መልስ የማይሰጥ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፍ ዘገባ ጎዶሎ ነው፡፡ አንባቢው፣ አድማጩም ሆነ ተመልካቹ የተሳተፈውን ሰው ቁጥር ማወቅ ያጓጓዋል። የዜና ኤዲተሮችም የዜናውን ዋጋ ከሚለኩባቸው መስፈርቶች አንዱ ይሄው ቁጥር ነው፡፡ በመሆኑም መሰል ሁነቶችን ለመዘገብ የተመረጠ ጋዜጠኛ፣ እንደምንም ብሎ የሆነ ቁጥር ይዞ መምጣት ይጠበቅበታል፡፡
ችግሩ ቁጥሩን ለመገመት ያለው ፈተና ብቻም አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በዘገባ ላይ የሚቀርቡ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፍ ተሳታፊዎች ቁጥር ጥያቄና ቅሬታ የሚነሳባቸው ናቸው፡፡ ምክነያቱም የሆነ ወገን ቁጥሩ እንዲበዛ፣ የሆነ ወገን ደግሞ እንዲያንስ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ጉዳዩ የጋዜጠኞች ፈተና የሚሆነው፡፡ በተቃውሞ ሰልፎችና በሌሎች መሰል ሁነቶች ላይ የተሳተፈውን እያንዳንዱን ሰው መቁጠርና፣ ‘ይሄን ያህል ህዝብ ተገኝቷል’ ብሎ መዘገብ ፍጹም የማይሞከር ነገር ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ግን እቅጩን ባይሆንም፣ ከትክክለኛው ቁጥር ጋር ተቀራራቢ የሆነ ግምት ለመስጠት የሚያስችሉ መላዎች እንዳሉ ጀሲካ ትጠቁማለች፡፡
በሙዚቃ ኮንሰርቶችና በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የተገኘውን ህዝብ ቁጥር ለማወቅ እምብዛም አዳጋች አይደለም፡፡ በስቴዲየሙ ወይም በአዳራሹ የመያዝ አቅም፣ በተቆረጠው ትኬት፣ በተያዘው ወንበር ወዘተ… አማካይነት በስነስርዓቱ ላይ የታደመውን ሰው መገመት ይቻላል፡፡ ድርጊቱ የሚከናወነው ከአዳራሽ ውጭ ወይም አደባባይን በመሳሰሉ ክፍት ቦታዎች ላይ ከሆነ ግን፣ የተገኘውን ሰው ብዛት መገመት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለነገሩ ለዚህም መላ አለው ባይ ናት ጀሲካ፡፡ ይህ መላ ‘ጃኮብስ ክራውድ ፎርሙላ’ ይሰኛል፡፡
ኸርበርት ጃኮብስ የተባሉ አሜሪካዊ የጋዜጠኝነት ፕሮፌሰር በ1960ዎቹ ያፈለቁት ይህ መላ፣ አደባባዩን ያጥለቀለቀውን ህዝብ በሙሉ መቁጠርን ግድ አይልም፡፡ ዘዴው ቀላል ነው፡፡ መጀመሪያ በተወሰነ ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ ያሉትን ሰዎች መቁጠር፡፡ ተመሳሳይ ስፋት ባላቸው ሌሎች የተወሰኑ ቦታዎች ላይም ተመሳሳይ ቆጠራ ማድረግ፡፡ የቁጥሩን ድምር ለቦታዎቹ ቁጥር በማካፈል አማካዩን ማስላት፡፡ በመጨረሻም ይህንን ቁጥር በአደባባዩ ስኩየር ሜትር ስፋት ማባዛት፡፡ ውጤቱ በአደባባዩ የተሰበሰበውን ሰው ብዛት ያመለክታል፡፡
ሌላው መገመቻ መላ ደግሞ ፎቶግራፍ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከፍ ካለ ቦታ ላይ ሆኖ ህዝቡን ሙሉ ለሙሉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ማንሳት። ከዚያም ፎቶግራፉን በሰንጠረዥ መከፋፈልና በአንዱ የሰንጠረዥ ክፍል ውስጥ ያለውን የሰው ብዛት፣ በሰንጠረዦቹ ክፍልፋዮች ቁጥር ማባዛት። ውጤቱ እቅጩን ባይሆንም፣ ከዝም ብሎ ግምት ለትክክለኛው የቀረበ የህዝብ ቁጥር ይሰጣል። እርግጥ ይሄኛው መላ የራሱ ችግሮች አሉበት፡፡ ክፍት የሆኑ፣ ከካሜራው እይታ ውጭ የሆኑና የተከለሉ ቦታዎችና ሰዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉና፡፡
ሰልፉ በጎዳና ላይ ከሆነም ሌላ መላ አለ፡፡ እዚህ ላይ ጋዜጠኞች ሰልፈኞች ከሚጓዙበት ጎዳና ዳር በመሆን ቆጠራ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት ግን፣ ጎዳናውን ሞልቶ የሚተመውን ህዝብ አንድ በአንድ መቁጠር አለባቸው አይደለም፡፡ እንዲህ ከሆነማ ምኑን ዘገቡት!... ቁጭ ብለው ሲቆጥሩ መዋላቸው ነው፡፡
 ጀሲካ እንደምትለው፤ ጋዜጠኞች ቀደም ብለው ከመንገዱ ዳር የቆጠራ ቦታ ያዘጋጃሉ፡፡ ሰልፈኛው ማለፍ የጀመረበትን ሰዓትና ደቂቃ ይመዘግባሉ፡፡ ከዚያም ለሶስት ያህል ጊዜ በተወሰነ ደቂቃ ውስጥ በመንገዱ የሚያልፈውን ሰልፈኛ ይቆጥሩና አማካዩን ያወጣሉ፡፡ ይህን አማካይ መነሻ በማድረግ ሰልፉ ተጀምሮ እስኪያልቅ በፈጀው ጊዜ ውስጥ በጎዳናው ላይ ያለፈውን ሰው ማስላት ይችላሉ፡፡
አንዳንዴ ደግሞ የሌሎችን ግምት መነሻ በማድረግ የራስን ግምት መስጠት አማራጭ ሊሆን ይችላል ትላለች ጄሲካ፡፡ ጋዜጠኞች በአንድ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፈውን ህዝብ ቁጥር በተመለከተ ከመንግስት፣ ከፖሊስ አካላት፣ ከሰልፉ አዘጋጆች ወዘተ… የተለያየ መረጃ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ ነገሩን በጥንቃቄ መመልከትና የራስን ድምዳሜ መስጠት ያሻቸዋል፡፡
ጋዜጠኞችን ከህዝብ ቁጥር ግምት ፈተና ይታደጋል የተባለው ሌላኛው መላ ግን፣ ቴፕሪከርደር እየተዋዋሰ ለሚሰራው የኛ አገር ጋዜጠኛ የሚሆን አይመስልም፡፡
ምክንያቱም ነገርየው በኮምፒዩተር የታገዘና በድረገጽ የረቀቁ የሂሳብ ስሌቶችን መስራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይጠይቃል፡፡ ፖፑላር ሜካኒክስ የተሰኘው ድረገጽ እንዳስነበበው፣ ተቀማጭነቱን በዋሺንግተን ዲሲ ያደረገው ‘ዲጂታል ዲዛይን ኤንድ ኢሜጅ ሰርቪስ’ የተባለ ተቋም፣ በሳተላይት ቴክኖሎጂ ከአየር ላይ በሚነሱ ፎቶግራፎች አማካይነት፣ በሰልፎች ላይ የተሳተፉ ሰዎችን በመቁጠር ዘገባ የመስራት አዲስ አማራጭ ለመተግበር ተፍ ተፍ ማለቱን ተያይዞታል፡፡
በተቃውሞ ሰልፍ የተሳተፉ የበእውቀቱ ስዩም ገጸባህሪ፣ “በሰልፉ ምን ይህል ሰው ተሳትፏል?” ተብለው ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ላብቃ…
“ከአምስት እስከ አምስት መቶ የሚገመቱ ሰልፈኞች ሳይሳተፉ አይቀሩም!”

Published in ህብረተሰብ

“ሞት የማያመልጡት ግዴታ ቢሆንም በአሟሟት ሊሸነፍ ይችላል”

       የ”አምላክ” ትልቁ ጥበቡ ሞትን መፍጠሩ ይመስለኛል፡፡ እያንዳንዱ ሃይማኖት እግሩን ያቆመው በሞት ላይ ነው፡፡ ሞት ባይኖር የሰው ልጅ፣ በአምላክ አያምንም ነበር። ሃይማኖቶች እግር ይከዳቸዋል፡፡ …ዘር ካልሞተ/ካልበሰበሰ ፍሬ አይሆንም፡፡ በዚህች ሰከንድ በሰውነታችን ውስጥ ህዋሳት እየሞቱ እራሳቸውን ባያድሱ ህልው መሆን አንችልም፡፡ ሞት እንደብዙዎቻችን እምነት፣ የህይወት ማብቂያ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ህያው አካል ውስጥ የተጐነጐነ ሞት አለ፡፡ ግልፅ ነው ሞት የሌለበት ህይወት፣ ህይወት ሊሆን አይችልም፤ ህይወትን ህይወት ያደረገው ሞት ነው፡፡ ስለዚህ ህይወት ሞት ነው፡፡ ወይም ሞት ህይወት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ህይወት፣ ህይወትና ሞት ነው፡፡ መወለድ የህይወት አካል እንደሆነው፣ ሞትም የህይወት አካል ነው፡፡ ህይወታችንን እንደምንኖር፣ ሞታችንን እንኖራለን፡፡ ሄራክሊተስ የተባለው ፈላስፋ፣ አማልክትን ሟቾች፣ ሰዎችን ግን ሞታቸውን ጭምር የሚኖሩ፣ ህይወታቸውን የሚሞቱ ዘላለማውያን ያደርጋቸዋል… እንዲህ ይላል፤ “gods are mortal, humans immortal, living their death, dying their life” ከሞት የሚያመልጥ ማንም የለም፤ ለሕያዋን ሁሉ የተሰጠ ስጦታ ነው፡፡ ዓለም እስካለች አለ፣ ዓለም ደግሞ ያለ ሞት አትኖርም፡፡ ሞት ሲሞት ዓለም ትሞታለች፡፡ ዓለም ስትሞት ሞት ይሞታል፡፡ “…አስር ዓመትም፣ መቶ ዓመትም፣ ሺ ዓመትም በሕይወት ብትኖር ከሞት ጋር ክርክር የለህም” (መፅሐፈ ሲራክ 41፣4) የሞት መልካምነት “Death destroys a man, but the idea of death saves him” E.M.Forster መፅሐፉ ሞት በአዳምና ሔዋን ጥፋት በኩል እንደመጣብን ይነግረናል፡፡ በልጅነታችን… “አዳምና ሄዋን ባጠፉት ጥፋት እኛ ላይ ደረሰ የዘላለም ሞት” ብለው እያዘመሩ የቄስ አስተማሪዎቻችን አዳምና ሄዋንን አስወቅሰውናል፡፡

እኔ ግን አዳምና ሄዋን ካመጡልን መልካም ነገር አንፃር ሊሸለሙ ይገባቸዋል ነው የምለው (እናመሰግናለን እሺ አዳምዬና ሄዋንዬ… ባላችሁበት ይመቻችሁ!) ለእግዜር ይህን የመሰለ ውለታ ውለውለት “ጥፉ ከዚህ” ብሎ ከገነት ማባረሩ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ሞት ባይኖር በእግዜር የሚያምን ማን ነው? ሃጢያት ብንሰራ አንሞት! (የሃጢያት ደሞዙ ሞት ነው ይለናል)… የንስሃ ጊዜ ያልፍብናል ብለን አንፈራ ነገር፣ ዘላለም ኗሪ ነን። እና ምን ፈልገን አምላክን እናምናለን፡፡ ከሞት በኋላ ያለ ህይወታችንን የተዋበ ለማድረግም አይደል የምናምነው? ሞት ከሌለ ታዲያ የምን ከሞት በኋላ ህይወት አለ፣ ለወዲያኛው ዓለም የተገባልን ቃል፣ ወዲያኛው ዓለም መሄድ የሚባል ነገር ስለሌለ አብሮ ይሞታል፡፡ በእርግጥ ግን በእምነቱ ከሄድን፣ ሞትን የፈጠሩት አዳምና ሄዋን ሳይሆኑ ፈጣሪ ነው፣ አዳምና ሄዋን የፈጠረውን ነው ያፀደቁት! እሱ ሞትን እፀበለሱ ውስጥ ጠቅልሎ አስቀመጠው፣ እነሱ በልተው ፈቱት (just if we take the Biblical point of view) ማንም ይፍጠረው፣ እንዴትም ይፈጠር ሞት አያሌ ጥቅሞች አሉት፡፡ አንዱ ከታካች ህይወት መገላገያነቱ ነው፡፡ ሰው መኖር ቢደክመው እራሱን ያጠፋል፣ ሞት ባይኖር ምን ያደርጋል? እኔ ግን የምር ሞት ባይኖር እራሴን የማጠፋ ነው የሚመስለኝ… (ውይይ ለካ ሞት የለም…) ለመሞት ብለን የተሰቀልንበት ገመድ የአንገት ጌጥ ብቻ ሆኖ ሊያርፍ ነው… መሞት እየፈለጉ፣ መሞት አለመቻል… ሲደብር!!! መፅሐፈ ጥበብ 7፣6 “…የሁሉም ወደዚህ ዓለም አመጣጡ አንዲት ናት፣ የሁሉም መምጣቱ እኩል ናት” ሌላው የሞት ጥቅም የእርጅና መድሃኒት መሆኑ ነው፡፡ ሞት ባይኖር እየጃጁ መኖር እንጂ መሞት አይታሰብም፡፡ ህዋሳትህ ደክመው፣ አይኖች ማየት ተስኗቸው፣ ጉልበት ከድቶህ ስትነሳም ስትቀመጥም ጫን ጫን እየተነፈስክ ትኖራታለህ እንጂ፣ ሞትን ብትለምንም አታገኘውም፡፡

እና ይህን ከመሰለው ኩነኔ መዳኛ አይደለምን? ለዚህ ተክለ ሐዋሪያት ተክለማሪያም፣ “ኦቶባዮግራፊ (የህይወቴ ታሪክ)” በተባለ መፅሐፋቸው ያሉትን ጠቅሼ ልለፍ፤ “ሞት የማይታለፍ እዳ የሆነበት ምክንያት ለካ እርጅናን ለማስወገድ ኖሯል… እንግዲያውስ ሞትን በጣም መጥላት ወይም መፍራት አያስፈልግም፡፡ ጥሩ መድሃኒት ነው፤ ያሳርፋል፡፡” (ገፅ 122) ግልግል ለፈለገውም አለሁ ባይ ነው ሞት፡፡ የሰው ፊት ከማየት ሞትን የመረጠው እንዲህ ይላል፤ “ሞት ይቅር ይላሉ ሞት ቢቀር አልወድም አፈሩ ድንጋዩ ከሰው ፊት አይከብድም” እና ከሰው ፊት ይቀለኛል ያለው ሞት ነው ይቅርበት የምትሉት? ይሄ ሰውዬ ምን አደረጋችሁ-- እስቲ? በስተእርጅናው ለህይወት ጨለምተኛ አመለካከትን የያዘው ጠቢቡ ሰለሞን፣ በመፅሐፈ መክብብ መፅሐፉ በምን እንደሚሻል ባይገልፅም፤ “ከመልካም ሽቶ መልካም ስም፣ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል” ይላል፡፡ ሞትን በአሟሟት! በብዙ ሰው ዘንድ፣ ከሞቱ አይቀር በአሟሟት ሞትን ማሳፈር ይቻላል ተብሎ ይታመናል። “አሟሟቴን አሳምርልኝ” ይላል የኛ ሰው። በጀግንነት ኖረው፣ ሞት ላይ ምላሳቸውን ሲያወጡ እድሜያቸውን አሳልፈው አሟሟታቸው የሚከፋባቸው አሉ፡፡ ጀግና የነበረን ሰው “አይሞቱ አሟሟት ሞተ… እምጵ!” ሲሉለት እንሰማለን፡፡

ይህ ከመሞትም ባለፈ፣ የአሟሟት አይነት እንዳለ ይነግረናል፡፡ የፈሪ ሞት፣ የጀግና ሞት፣ ድንገቴ ሞት፣ አስገራሚ ሞት፣ አሰቃቂ ሞት… እንዲህ ነው የማይሉት ሞት አለ፣ አሉ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ”መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው መፅሐፋቸው፤ “ሞት የማያመልጡት ግዴታ ቢሆንም በአሟሟት ሊሸነፍ ይችላል” (183) ይላሉ፡፡ ገጣሚው ደግሞ እንዲህ ይላል፣ “አሁን የኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ ጉች ጉች ያለ ጡት አንድ ቀን ሳላይ” የዚህ ደግሞ የተለየ ነው፣ ጉች ጉች ያለ ጡት አንድ ቀን ባለማየቱ አሟሟቱን አይረቤ ያደርገዋል። ምስኪን! ምናለ በዚህ በኛ ዘመን ተወልዶ ባየው… ጉች ጉች ያለ ጡት በየመንገዱ እዩኝ እዩኝ እያለ ሲማጠን ኖሮ ቢሆን አሟሟቱን በምን ይወቅስ ነበር? መቼም የዛሬ ጡት ከመታየት ወደ ማየት ተሸጋግሯል አይደል፡፡ ሰዎች በአሟሟታቸው ምክንያት ይጀግናሉ። የጀግና ሞት ይባልላቸዋል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስን ጀግንነት ከፍታ ከሰጡት ነገሮች አንዱ አሟሟታቸው ነው፡፡ ሟች አሟሟቱ የፈሪ ከሆነ ደግሞ ይነቀፋል። ዮፍታሔ ንጉሴ በ”አፋጀሽኝ” ቲያትሩ እንዲህ ይለዋል ፈሪውን ሟች፤ “ምንተ ሊቁ፣ ምንተ ሊቁ፣ ምንተ ላሊበላ! ሲሸሽ የሞተ ሰው ተስካሩ፣ ሲሸሽ የሞተ ሰው ተስካሩ አይበላ” ፍትህ የማያውቅ ሞትም አለ፡፡

ፊቱ ሲንጐማለሉበት ዝም ብሎ፣ በሌላ ጊዜ ተልከስክሶ የሚመጣ፣ አልከስክሶ የሚገድል፡፡ እንዲህ ይላል ዮፍታሄ በሌላ ግጥሙ፤ “ዋናውስ በሽታ ምንም አልነካቸው ካገገሙ ኋላ ግርሻ ገደላቸው” ሞት ፈሩትም ደፈሩት ያው ሞት ነው፡፡ የማይቀርን ነገር ከመፍራት ግን በተዛና መንፈስ መቀበሉ የተሻለ ነው፡፡ ሞትን ማወቅ፣ መቀበል… “የሰው ልጅ የመጨረሻው ጥበብ ላይ ደረሰ የሚባለው ሞት መኖሩን ሰያውቅና ሲረዳ ነው” (እኔና ቹ፣ 164) ምን ማለት ነው? ሞት መኖሩን የማያውቅ ሰው አለ፤ አዎ! የማያውቁ ሰዎች አሉ፡፡ በእርግጥ የማያውቁ ከማለት የሚዘነጉ ብንላቸው ይሻላል፡፡ ዘላለም የሚኖሩ ይመስል ሀብት ያጋብሳሉ፣ ይነጥቃሉ። እገድላለሁ ብለው ይፎክራሉ፣ እገድላለሁ ብሎ መሞት እንዳለ ግን ለአፍታም ትዝ አይላቸውም፡፡ ህይወት ሞትን ጨምሮ አይመስላቸውም፣ የሌላው እንጂ የነሱ ሟችነት ትዝም አይላቸው፡፡ የሰው ልጆች በሙሉ ሞትን ቢያውቁ እና ቢረዱ ምድር እጅግ የተዋበች ትሆን ነበር፡፡ ብዙዎች ግን ሌሎች ይሞታሉ እንጂ እነሱ ዘላለማዊ የሚሆኑ ይመስላቸዋል፡፡ ዘርማንዘራቸው በልቶ የማይጨርሰውን ሀብት ሲያከማቹ፣ ለመቼ የሚል ጥያቄ ለአፍታ አዕምሯቸው ውስጥ አይመጣም፡፡ ሞትን ለማወቅና ለመረዳት የሞት ፍርሃትን ማስወገድ ያስፈልጋል (መጀመሪያውንስ ሞት ምኑ ያስፈራል!) ሞት ሊፈራ እንደማይገባ ከሰበኩ ፈላስፎች አንዱ የግሪኩ ኢፒኩረስ ነው። ሊጐዳን እንደማይችል ለማሳየት እቺን አመክንዮ ያስቀምጣል፤ “For when you are, death is not, and when death is, you are not. Therefore, death can not harm you” ይሄው ፈላስፋ (ኢፒኩረስ) የፍልስፍና ዓላማ፣ የደስታ መሰናክል የሆነውን የሞት ፍርሃት በማስወገድ ደስታን እውን ማድረግ እንደሆነ ያምናል፡፡ “በሃይማኖት ምክንያት የተፈጠረብን የሞት ፍርሃት ተረት ነው” ሲልም ይናገራል፡፡ “Death is not evil” ይላችኋል ከፈለጋችሁ፡፡

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በ”ስልጣን ባህል እና አገዛዝ” መፅሐፋቸው ይህን ይላሉ፤ “ልደት የሞት ዋዜማ ነው፤ ህይወት የሞት ጥሪ ነው፣ ኑሮ የሕይወት ፃዕር ነው፡፡ ሰው መሆን ይህንን እውነት ማወቅ ነው”ሰው ለምን ሞትን ይፈራል? አንደኛው ምክንያት ከሞት በኋላ ያለውን ህይወት አለማወቁ ነው። ሁለተኛ ኢፒኩረስ እንዳለው፣ በሃይማኖቶች ምክንያት የሚፈጠርበት የሞት ፍትሃት አለ፣ ተቃጥልክ ነደድክ፣ ነፈርክ እያሉ ልቡን በፍርሃት ያነዷታል፡፡ ለዛ ሲል ከሞት በኋላ ዋስትና ይሆነኛል ብሎ ለሚያስበው አምላክ ይንበረከካል፡፡ ግንኙነቱ ከለላ ፍለጋ ይሆናል፡፡ ስሙም እምነት ይባላል፡፡ እዚህ ጋ ግን አንድ ጥያቄ እናንሳ፡- አዳምና ሄዋን እፀ በለሲቷን በመብላታቸው ምክንያት ሞት መጣባቸው፡፡ እሺ ይሁን… ሌሎች እንስሳትስ ምን ስለበሉ ሞት መጣባቸው? ሞት የመጣው እፀ በለሲቷን በመብላት ከሆነ፣ ያልበሉት ላይ እንዴት ሊመጣ ቻለ? ወይስ እንስሳት ከአዳም ጋር አንድ ሆድ ነበር የሚጋሩት? 

Published in ህብረተሰብ
Page 6 of 19