“ቤቱ የዘገየው በትራንስፎርመር ችግር ነው” ዩኒቨርሲቲው

ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከሁለት ዓመታት በፊት በ156 ሚሊዮን ብር ለመምህራን የገዛቸውን መኖሪያ ቤቶች በወቅቱ ባለማስረከቡ መምህራኑን ከማስቆጣቱ በተጨማሪ ኪሳራ እየደረሰበት ነው፡፡
የዩኒቨርስቲው ስትራቴጂክ ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሞላ አባቡ በበኩላቸው፤ በከተማው የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ችግር ስለነበረ እስኪሟላ ድረስ የመኖሪያ ቤቶቹ ርክክብ ዘግይቷል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርስቲው ከሁለት አመት በፊት በአራት ቦታ የኮንዶሚኒየም (የጋራ መኖሪያ) ቤቶችን   ከከተማው አስተዳደር ቢገዛም እንዳላስረከባቸው የገለፁት መምህራን፤ ቤቶቹ ለብልሽት እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው ቤቶቹን በአፋጣኝ በማስረከብ እኛን ከቤት ችግር፣ ቤቶቹንም ከብልሽት ሊታደጋቸው ይገባል ብለዋል መምህራኑ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከ1500 በላይ መምህራን እንዳሉትና ለመምህራኑ በየወሩ በአማካይ 600 ብር የቤት ኪራይ አበል እንደሚሰጥ መምህራኑ ጠቅሰው፤ ቤቶቹን ባለማስረከቡ በአመት ወደ 11 ሚሊዮን ብር ገደማ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡  
ዩኒቨርስቲው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ቤቶችን ከከተማ አስተዳደሩ የገዛው ለከተማው ህዝብ ተብሎ ከተገነባው ላይ መሆኑን የገለፁ መምህራን፣ ወይ ህዝቡ አልተጠቀመ ወይ መምህራኑ ከቤት ኪራይ አላረፉ፤ ቤቶቹ ከሁለት አመት በላይ ያለ አገልግሎት እየተሰነጣጠቁና እየተበላሹ ነው ብለዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሞላ አባቡ፤ ርክክብ ሳይፈፀም ቤቶቹ ያለ አገልግሎት መቀመጣቸውን ጠቅሰው፣ ከትራንስፎርመር ችግር በተጨማሪ ቤቶቹን ከከተማው አስተዳደር ለመቀበልም ብዙ ጊዜ እንደወሰደ ተናግረዋል፡፡ “መጀመሪያ ለቤቶቹ የተጠየቅነው 99 ሚሊዮን ብር ነበር” ያሉት አቶ ሞላ፤ ቤቶች ልማት መስሪያ ቤት “ዋጋውን ስናሰላ ስህተት ፈጽሜያለሁ” በማለት ክፍያውን ወደ 156 ሚሊዮን ብር ለውጦብናል ብለዋል፡፡ “የቤቶቹ ዋጋ በዚህ መጠን ሲጨመርብን ከገንዘብ ሚኒስቴር በጀት ማስፈቀድና ከቤቶች ልማት መስሪያ ቤት ጋር ሌላ አዲስ ውል መዋዋል ነበረብን፣ ይህም ሂደቱን አጓትቶብናል ብለዋል፤ ምክትል ፕሬዚዳንቱ፡፡
ትራንስፎርመሩን በተመለከተ ከከተማው መብራት ሃይል ጋር በመነጋገር ዩኒቨርስቲው ክፍያ መፈፀሙንና የውሃ መስመር ዝርጋታውም መሠራቱን የጠቆሙት አቶ ሞላ አባቡ፤ የቤቶች ልማት በበጀት እጥረት ያላጠናቀቃቸው የማሳረጊያ ስራዎችን ማለትም የበር፣ የመስኮት፣ የወለል፣ የኮርኒስና መሰል ስራዎችን ለማሰራት ዩኒቨርስቲው ጨረታ አውጥቶ በሂደት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ቤቶቹን መቼ ለመምህራኑ ማስረከብ እንደሚቻል የተጠየቁት አቶ ሞላ፤ በእርግጠኝነት ለመናገር እንደሚያስቸግር ገልፀው፤ ነገር ግን ስራው ሊጠናቀቅ ተቃርቧል፤ እያንዳንዱ መምህር ምን አይነት ቤት እንደሚረከብ ከነስፋቱ እንዲያውቅ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ቤቶቹ ሲጠናቀቁ ከ1300 በላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ከቤት ችግር እንደሚላቀቁ አቶ ሞላ የገለፁ ሲሆን፤ መምህራኑ በበኩላቸው የትራንስፎርመር እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናቅቀዋል በማለት “ርክክቡ ያለ በቂ ምክንያት መጓተቱን ይናገራሉ፡፡

Published in ዜና

ዳሽን ባንክ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን “የዓመቱ ብቸኛው ምርጥ ግብረ ሰናይ ድርጅት” አድርጐ በመምረጥ፣ የ500ሺህ ብር ሽልማት ሰጠ፡፡   
ባንኩ፤ ማዕከሉ የሚያበረክተውን ማኅበራዊና ሰብአዊ አስተዋጽኦ በጥልቀት በማጤን፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት፣ የተጠቀሰውን ገንዘብ እንዳበረከተ ገልጿል፡፡ አምናም ባንኩ ለ“መቄዶንያ” 200ሺ ብር መስጠቱ ይታወሳል፡፡
የአቅመ ደካማና ሕሙማን መርጃ ማዕከሉ፣ በአሁኑ ወቅት፣ ምንም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን፣ በተለይም ራሳቸውን ችለው መፀዳዳት፣ መመገብና መንቀሳቀስ የማይችሉ ከ300 በላይ የአልጋ ቁራኛ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማንን ከወደቁበት ጐዳና በማንሳት፣ ተገቢውን እንክብካቤና ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፤ በሚቀጥለው ዓመት የተረጂዎቹን ቁጥር 600 ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጿል፡፡ ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ እንዲረዳው ታኅሣሥ 13 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 እስከ 12፡00 በግሎባል ሆቴል የገቢ ማሰባሰቢያ ማዘጋጀቱን የገለፀው ማዕከሉ፤ ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች በስፍራው በመገኘት ድጋፍ እንዲያደርጉ በአረጋውያኑና በሕሙማኑ ስም ጠይቋል፡፡  


Published in ዜና


በፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ከሌሎች ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ጋር በመጀመሪያ ተጠሪነት በሶስት መዝገቦች የተከሰሱት አቶ መላኩ ፈንታ ከሚኒስትርነታቸው ጋር ተያይዞ ለተነሣው ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ረቡዕ እለት የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል ሲል ብይን ሠጥቷል፡፡
ቀደም ሲል ሠኞ ህዳር 9 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት፣ አቶ መላኩ ፈንታ ባቀረቡት መከራከሪያ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆናቸውን በማስረዳት ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊታይ እንደሚገባ የገለፁ ሲሆን አቃቤ ህግ በጉዳዩ ላይ በሠጠው አስተያየት፤ ተከሣሹ በእርግጥም በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ም/ቤት አባል መሆናቸውን ተቀብሎ፣ ነገር ግን የሚመሩት መስሪያ ቤት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባለመሆኑ፣ ተጠቃሹ ያላቸው የሚኒስትር ማዕረግነት ለጥቅማ ጥቅም አላማ ብቻ የሚያገለግል እንደሆነ አስረድቷል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለረቡዕ ህዳር 11 ቀን 2006 ቀጠሮ የሠጠ ሲሆን ረቡዕ እለት የዋለው ችሎትም መዝገቡ የተቀጠረው በፍርድ ቤቱ የቀረበውን ጉዳይ ከማየት ስልጣን ጋር ተያይዞ በተነሣው ጭብጥ ላይ ብይንና ትዕዛዝ ለመስጠት መሆኑን አስታውቆ ብይን ሠጥቷል፡፡
ፍ/ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለው የትኛው ፍ/ቤት ነው የሚለው ሣይረጋገጥ ወደ ክርክር መግባት አይቻልም ካለ በኋላ፣ በተነሣው መከራከሪያ ጭብጥ መሠረት፣ አቶ መላኩ ሚኒስትር ናቸው ወይስ አይደሉም? ሚኒስትር ከሆኑስ ጉዳዩን አከራክሮ የመወሠን ስልጣን ያለው የትኛው ፍ/ቤት ነው የሚለው የግድ እልባት ማግኘት አለበት ብሏል።
ፍ/ቤቱም አቶ መላኩ ፈንታ በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆናቸውን ከግራ ቀኙ ክርክር እና ከተለያዩ ሠነዶች ማረጋገጡን በብያኔው አስታውቆ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የስነ ስርአትና የማስረጃ ህግ አዋጅ መሠረት፤ የፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት (ሚኒስትሮች ጨምሮ) በስራ ሃላፊነታቸው ምክንያት ተጠያቂ በሚሆኑባቸው ሙስናን ጨምሮ ማናቸውም የወንጀል ጉዳዮች የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ የስረ-ነገር ስልጣን የተሰጠው መሆኑ በግልፅ ስለ ደነገገ፣ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ነው ብሏል፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ሁለት አዋጆች ሁለት ንኡስ አንቀፆች ህገ-መንግስታዊ ናቸው? አይደሉም? የሚለው ትርጉም የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው ብሏል - ፍ/ቤቱ፡፡
በተለይ የአቶ መላኩ ጉዳይ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚታይ ከሆነ፣ በህገ መንግስቱ የተከበረላቸውን መሠረታዊ ጉዳያቸውን በይግባኝ እንዲታይ የማቅረብ መብት በግልፅ የሚጋፋ መሆኑን ያመላከተው የፍ/ቤቱ ብይን፤ አቶ መላኩ በዋና ወንጀል አድራጊነት ከሌሎች ሠዎች ጋር ተጣምሮ የወንጀል ክስ የቀረበባቸው በመሆኑና የሁሉም ተከሣሾች ጉዳይ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ቢታይ ሁሉም ተከሣሾች በህገ መንግስቱ የተከበረውን የይግባኝ ጉዳይ የማቅረብ መብት በግልፅ የሚጋፋ ከመሆኑም ሌላ የአቶ መላኩ ጉዳይ ብቻውን ተነጥሎ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት እንዲሁም ከእሣቸው ጋር የተከሠሡት ሌሎች ተከሣሾች ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ተነጥሎ ይታይ ቢባል ደግሞ ሁሉም ሠዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማናቸውም አይነት ልዩነት ሣይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል ከሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 25 መሠረታዊ መርህ ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑን ፍ/ቤቱ በብይኑ አትቷል፡፡ ይሄ ማለት፣ አቶ መላኩ በጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳያቸው ይታይ ቢባልና ሌሎች ተከሣሾች ተነጥለው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ጉዳያቸው ይታይ ቢባል፣ ሌሎች ይግባኝ የመጠየቅ መብታቸው ሲከበርላቸው፣ አቶ መላኩ የይግባኝ መብት እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ይሆናል፡፡ የአቶ መላኩም ሆነ የሌሎች ተከሣሾች ሠብአዊ መብት በእኩል እንዲጠበቅ አከራካሪው ጉዳይ የህገ-መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል ብሏል፡፡ በዚህ መሠረት የህገ መንግስታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሣኔ ሊያገኝ የሚገባ በመሆኑ፣ የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፣ ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች የማጣራት ሃላፊነት የተጣለበት በመሆኑና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የስነ ስርአትና የማስረጃ ህግ አዋጅ ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 20(6)፣ አንቀፅ 25፣ አንቀፅ 10 እና አንቀፅ 13(1) ይቃረናሉ ወይስ አይቃረኑም? እንዲሁም የስረ ነገሩ ስልጣን የየትኛው ፍ/ቤት ነው? የሚለውን እንዲመረምርና ትርጉም እንዲሠጠው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ጉዳዩ ሊመረመር እንደሚገባ በማመን፣ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ፍ/ቤቱ በይኗል፡፡
ፍ/ቤቱ በሠጠው ትዕዛዝም የብይኑ ትዕዛዝ ግልባጭ በመሸኛ ለፌደሬሽን ም/ቤት ፅ/ቤት እና የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ፅ/ቤት በእለቱ እንዲላክ በማለት ለታህሣስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
በፍ/ቤቱ ብይንና ትዕዛዝ ዙሪያ የህግ ትንታኔ እንዲሠጡን ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የህግ ምሁራን፤ እንዲህ አይነቱ ብይን ከዚህ ቀደም በእነ አቶ ታምራት ላይኔ እና አቶ ስዬ አብርሃ ላይ ተግባራዊ ተደርጐ እንደነበር በመጠቆም፣ ፍ/ቤቱ ህገ መንግስታዊ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የሚላቸውን ጉዳዮች በራሱ ከመወሠኑ በፊት ለሚመለከተው አካል መምራቱ ተገቢ ነው ብለዋል።  

Published in ዜና

የሽብርተኝነት ክስ ቀርቦበት የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት የአንድነት ፓርቲ አመራር አንዷለም አራጌ፤ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ የፃፈው “ያልተሄደበት መንገድ” የተሰኘ መጽሐፍ መታተሙ የሚታወቅ ሲሆን፤ ነገ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት እንደሚመረቅ ፓርቲው አስታወቀ፡፡
የአንዷለም አራጌ ባለቤትን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኛ ቤተሰቦች በምረቃው ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል ያሉት የፓርቲው ተወካይ አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ በመጽሐፉ ላይ ከአቶ አስራት አብርሃም ትንታኔ በተጨማሪ ታዋቂ ግለሰቦች የውይይት ሃሳብ እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል፡፡
“ምረቃውን የምናዘጋጀው፤ አንዷለም በእስር ቤት ሆኖ ይህን የመሰለ መጽሐፍ በመፃፉ ለማበረታታትና አጋርነታችንን ለመግለጽ ነው” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ የአስር ቤቱን ችግሮችና የእስረኛ ስለላን ተቋቁሞ መጽሐፉን ለህትመት ማብቃቱ ያስደንቃል ብለዋል፡፡          

Published in ዜና

የአውሮፓ ህብረት 5.3 ቢሊዮን ብር የልማት እርዳታ ለኢትዮጵያ የሰጠ ሲሆን፤  የልማት እርዳታው ኢትዮጵያ ለምታካሂደው መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የትምህርት የጤናና መሰል መሰረታዊ አገልግሎቶች ግንባታና ጥበቃ፣ለድርቅ መከላከያና መቋቋሚያ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምታደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ማስፋፊያ የሚውል እንደሆነ ታውቋል፡፡
ከህብረቱ የኢትዮጵያ ልዑክ ፅ/ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከተሰጠው የ5.3 ቢሊዮን ብር የልማት እርዳታ ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ኢትዮጵያ ለምታካሂደው መጠነ ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ሲውል፣ አንድ ቢሊዮን ብር ደግሞ ድርቅን ለመከላከልና ለመቋቋም ለሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ የሚውል ነው፡፡ የተቀረው ገንዘብ ደግሞ ለጤና፣ለትምህርትና መሰል መሰረታዊ አገልግሎቶች ግንባታና ጥበቃ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚውል ታውቋል፡፡ የልማት እርዳታው ስምምነት የአውሮፓ ኮሚሽን የልማት ኮሚሽነር አንድሪስ ፒባልግስና በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ደኤታ አቶ አህመድ ሽዴ መካከል የፊታችን ሰኞ ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ግንባር ቀደም ከሆኑት የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች መካከል ዋነኛው ሲሆን የህብረቱና የኢትዮጵያ የልማት ትብብር ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ የልማት እንቅስቃሴ በገንዘብና በቴክኒክ ሲረዳ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

Published in ዜና

እስካሁን ከ40 በላይ የውጭ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ታውቋል
ለባዛሩ ፒስኩየሮች ይመጣሉ ተብሏል

የፈረንጆች አዲስ አመት፣ የፈረንጆች ገና እና የኢትዮጵያ የገና በዓል አንድ ሰሞን የሚከበሩበት የገናን ባዛርና ኤግዚቢሽንን ለማዘጋጀት በወጣው ጨረታ “አፍሮ ዳን” በ3.8 ሚሊዮን ብር ማሸነፉ ተገለፀ፡፡
የድርጅቱ ሀላፊዎች ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ እስካሁን በባዛሩ ላይ ለመሳተፍ 400 ኩባንያዎች የተመዘገቡ ሲሆን የውጭ አገር ነጋዴዎች 47 ቦታዎችን መያዛቸውን የ “አፍሮ ዳን” ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ወርቅሸት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ነጋዴዎቹ ከግብፅ፣ ከቱርክ፣ ከህንድና ከቻይና እንደሚሳተፉ የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ ከአገር ውስጥም ከ10 በላይ አልባሳት አምራቾች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ በአብዛኛው በቤት እቃ፣ በምግብ፣ በሙሽራ ልብስ፣ በህፃናት አልባሳት፣ በፋስት ፉድ፣ በስጦታ እቃዎችና በመሰል ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡ የባዛሩን የመዝናኛ ዘርፍ በተመለከተ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ሙዚቀኞች እንደሚሳተፉ የተናገሩት የመዝናኛው ዘርፍ ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ቴዲአብ፤ በመስከረም አጋማሽ ላይ በሚሌኒየም አዳራሽ ስራቸውን ያቀረቡት ፒስኩየሮች እንደሚሳተፉ በመግለጫው ላይ አስታውቀዋል፡፡ 30 ት/ቤቶች በዳንስ፣ በስዕልና በሌሎች ዘርፎች የተሰጥኦ ውድድር እንደሚያደርጉና አሸናፊዎች እንደሚሸለሙ የተገለፀ ሲሆን ይሄም ባዛሩን ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ለየት እንደሚያደርገው ተነግሯል፡፡ በፊት በርካታ ጠጅ አቅራቢዎች በባዛሮች ላይ ይሳተፉ እንደነበር ያስታወሱት የባዛሩ አሸናፊዎች፤ ይሄም ለመሳከርና ለብጥብጥ ይዳርግ ነበር በማለት አሁን ግን ሶስት ጠጅ አቅራቢዎች ብቻ እንደሚገቡ ጠቁመዋል፡፡ የፀጥታን ጉዳይ በተመለከተም ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሆነ የድርጅቱ ባለቤት ተናግረዋል፡፡ የባዛሩን ጨረታ በ3.8 ሚሊዮን ብር ገደማ ቢያሸንፉም ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ የ6 ሚሊዮን ብር  እንደሆነ የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ በባዛርና ኤግዚቢሽኑ ላይ ባህላቸውንና እሴታቸውን እንዲያስተዋውቁ ለ102 ኤምባሲዎች ግብዣ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡ ባዛርና ኤግዚቢሽኑን ፋፋ፣ ቃሊቲ ብስኩት፣ አምባሳደር ልብስ ስፌት፣ ቴክኖ ሞባይል፣ ኤልጂ ኤሌክትሮኒክስና የተለያዩ ቢራ ፋብሪካዎች ስፖንሰር እንዳደረጉት ታውቋል፡፡
ጨረታውን በምን መስፈርት እንዳሸነፉ የተጠየቁት አቶ ዳንኤል፤ “በፊት በፕሮፖዛል ነበር፤ አሁን ግን በገንዘብ ሆኗል፤ ስለዚህ በገንዘብ ብልጫ አሸንፈናል” ቢሉም እነሱ ግን ውድድሩ በፕሮፖዛል ቢሆን ይመርጡ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

Published in ዜና

በአዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ እምብርቱ ላይ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክስ ኮሚሽን ፊት ለፊት በ700 ሚሊዮን ብር የተሠራው ባለ 5 ኮከብ ዘመናዊ ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ዛሬ ይመረቃል፡፡
አቶ ገምሹ በየነ የተባሉ ባለሀብት ግዙፍ ኢንቨስትመንት የሆነው ባለ 10 ፎቅ መንትያ ሆቴል፤ 154 ክፍሎች ሲኖሩት የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራው መሳሪያ የተገጠሙለት መሆኑ ታውቋል፡፡
ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል፤ ሁለት ፕሬዚዴንሻል ክፍሎችና 16 ጁንየር ሱት፣ ስታንዳርድ፣ ኪንግ ሳይዝ፣ ደብል ትዊን፣ ፔንት ሃውስ ክፍሎች፣ አሉት፡፡ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሬስቶራንትና ባር፣ የሕፃናት መጫወቻ፣ የወጣቶች የኦሎምፒክ ደረጃ መዋኛ፣ ስፓና ጂምናዚየም…አለው፡፡
ሆቴሉ 10ኛ ፎቅ ፕሬዚዴንሻል ሱት ላይ ሆነው በሁሉም አቅጣጫ ከተማዋን እየቃኙ ለመዝናናት ያመቻል፡፡ ቀልብን የሚስቡት የመኝታ ክፍሎቹ፤ መታጠቢያ ገንዳና ሻወር፣ ብሮድ ባንድ ኢንተርኔት፣ 42 ኢንች ቴሌቪዥን ሳተላይት ቲቪና ስልክ፣…አላቸው፡፡
ኢሊሌ ሆቴል ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ዲፕሎማቶች፣ ኢንቨስተሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና፣ ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት ዛሬ እኩለ ቀን ላይ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡
ሆቴሉ፣ በአሁኑ ወቅት ለ300 ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር የሠራተኞቹ ቁጥር 450 እንደሚደርስ የሆቴሉ ባለቤት አቶ ገምሹ በየነ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

በተለያዩ ከተሞች በራሳቸው፣ በባለቤታቸውና በልጆቻቸው ስም 17 ቦታዎችንና ቤቶችን ይዘዋል ከሚለው ክስ ነፃ ሆነዋል፡፡
ከባለቤታቸው ጋር ምንጩ ያልታወቀ 490ሺ ብር በባንክ አንቀሳቅሰዋል ከሚለው ክስ ነፃ ናቸው ተብሏል

የቀድሞው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ያረጋል አይሸሹም፤ በፀረ ሙስና ኮሚሽን ከቀረቡባቸው አምስት ክሶች መካከል በአንዱ ብቻ “ጥፋተኛ ናቸው” የተባሉ ሲሆን፣ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አካብተዋል በሚል ከቀረበባቸው ክሶች ነፃ ሆኑ፡፡
አቶ ያረጋል አይሸሹም እና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ሃብታሙ ሂካ፣ ከሁለት የግል ድርጅት ሃላፊዎች ከአቶ ጌዲዮን ደመቀና ከቶ አሰፋ ገበየ ጋር “ጥፋተኛ ናቸው” የሚል ውሳኔ የተላለፈባቸው፤ ለሦስት የትምህርት ተቋማት ግንባታ ከወጣው ጨረታ ጋር በተያያዘ ክስ ነው፡፡ ህገወጥ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር  ለመምህራን ኮሌጅ፣ ለአዳሪ ት/ቤት እና ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የግንባታ ጨረታ ከመንግስት መመሪያ ውጪ እንዲከናወን አድርገዋል በሚለው ክስ 4ቱ ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው እንደተገኙ የከፍተኛው ፍ/ቤት ችሎት ሐሙስ እለት ገልጿል፡፡ 

አቶ ያረጋል እና አቶ ብርሃኑ ለተቋማቱ ግንባታ  የተመደበው ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን እያወቁ በግልጽ ተወዳዳሪዎችን ጋብዘው ማጫረት ሲገባቸው፣ የሶስቱንም ፕሮጀክቶች የዲዛይን፣ የቁጥጥር እና የኮንትራት ጨረታ በህገወጥ መንገድ ለጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት በጥቅሉ በ250ሺህ ብር ሰጥተዋል ይላል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ያቀረበው ክስ፡፡ አቶ ያረጋል ስልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም ጨረታዎቹ  አቶ ሃብታሙ በሚመሩት የትምህርት ቢሮ በኩል እንዲከናወኑ አድርገዋል የሚለው የኮሚሽኑ ክስ፣ መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ ስራው  በ “ውስን ጨረታ” እንዲከናወን በደብዳቤ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ብሏል፡፡  ለዚህ ወረታም አቶ ያረጋል ከ3ኛ ተከሳሽ ከአቶ ጌዲዮን ደመቀ፤ 50ሺህ ብር እንዲሁም አቶ ሃብታሙ 75ሺህ ብር እጅ መንሻ መቀበላቸው በክሱ ተገልጿል፡፡
“ጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት” ፕሮጀክቶቹን የመምራት አቅም እንደሌለው እያወቁ ውል የፈረሙት አቶ ጌዲዮንና ወኪላቸው አቶ አሰፋ ገበየሁ፤ ስራውን ለ5 ዓመታት በማጓተት መንግስትን ለ2.8 ሚ.ብር ተጨማሪ ወጪ ዳርገዋል ብሏል - የፀረ ሙስና ኮሚሽን፡፡

ፍ/ቤቱም በአራቱ ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ባለስልጣናቱና ፕሮጀክቶቹን እንዲመራ የተደረገው አማካሪ ድርጅት፤ በህገወጥ የጥቅም ትስስር፣ የትምህርት ተቋማቱን ግንባታ ለሦስት ድርጅቶች ሰጥተዋል የሚለው ፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ የሚመሩት “ጋድ ኮንስትራክሽን” በ40 ሚ. ብር የአዳሪ ት/ቤትና በ18ሚ ብር የመምህራን ኮሌጅ እንዲገነባ፣ አቶ መክብብ የሚመሩት ንብረት ለሆነው “ኮለን ኮንስትራክሽን” ደግሞ በ17 ሚ. የቴክኒክና ሙያ ተቋም እንዲገነባ በመስጠት ስራው አጓትተዋል ብሏል፡፡
አቶ ያረጋል አይሸሹም ከዚህ ክስ ነፃ መሆናቸውን ፍ/ቤቱ ገልፆ፣ የትምህርት ቢሮ ሃላፊና አራቱ የግል ድርጅት ሃላፊዎች ግን ጥፋተኛ ናቸው በማለት ወስኗል፡፡

ሌላኛው ክስ፣ አቶ ያረጋል፣ እንዲሁም የትምህርት ቢሮ ሃላፊውና ወንድማቸው ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አካብተዋል የሚል ነው፡፡
ርዕሠ መስተዳደር በነበሩበት ወቅት ደሞዛቸው 4500 ብር እንደነበረና ከዚያም  የፌደራል የህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሲሠሩ 5670 ብር ደሞዝ ይከፈላቸው እንደነበረ የሚገልፀው የኮሚሽኑ ክስ፣ ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ሃብት አካብተዋል በማለት ከሷቸዋል፡፡

አቶ ያረጋል በራሳቸው ስም በአዲስ አበባ በተለያዩ ከተሞች አራት ቦታዎችንና ቤት ይዘዋል የሚለው የክስ ዝርዝር፣ በባለቤታቸው ስም ደግሞ በ7 ሚሊየን ብር የሚገመት ሆቴልና ድርጅት እንዲሁም ስምንት ቦታ፣ የንግድ ሱቆችና ቤቶችን ቦታዎችን በተለያዩ ከተሞች ይዘዋል ይላል፡፡ በቤንሻንጉል ውስጥም በሁለት ልጆቻቸው ስምም 5 ቦታዎች ይዘዋል፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ቅርንጫፎች በራሣቸው እናበባለቤታቸው ስም ከ490 ሺ ብር በላይ አንቀሳቅሰዋል ብሏል - ፀረ ሙስና ኮሚሽን፡፡

የባለስልጣናት ሃብት ምዝገባ ሲከናወን ሃብታቸውን ሙሉ በሙሉ አላሣወቁም የተባሉት አቶ ያረጋል፤ “ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አካብተዋል” የሚለውን ክስ በበቂ ማስረጃ መከላከል በመቻላቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍ/ቤቱ ወስኗል፡፡

የትምህርት ቢሮ ሃላፊውም እንዲሁ ከወንድማቸው ጋር ከተመሳሳይ ክስ ነፃ ሆነዋል፡፡ ፍ/ቤቱ በሁሉም ክሶች ላይ ውሳኔ ያስተላለፈበትን ባለ 170 ገጽ ትንተና በንባብ ለማሰማት ሁለት ቀን ፈጅቶበታል፡፡
የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠባቸው ክሶች ላይ ከከሳሽ እና ከተከሳሽ የቅጣት አስተያየት ለመቀበል ለህዳር 26 ቀን ተቀጥሯል፡፡

Published in ዜና

የደብረ ብርሃን ጉዞዬን ያጠቃለልኩ የእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ድርጅትን የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፤ ከጋሽ ዓለማየሁ (ከሥ/አስኪያጁ) ጋር ጐብኝቼ ነው፡፡ ከተማው ውስጥ የሚሠራው የግብርናና የልማት ሥራ ሁሉ በሠርቶ ማሳያ ሞዴል መልክ ግቢው ውስጥ ይታያል፡፡ የመኖ ልማት አለ፡፡ የከብት እርባታ ከነወተት ተዋጽኦ ምርት ጥቅሙ፣ በባዮ ጋዝ የሚለማው መኖ፣ አልፋ አልፋ፣ የከብት ድንች፣ ቃሪያ ቲማቲም፣ የክብሪት ዛፍ፣ ጥቁር እንጨት ወዘተ አለ፡፡ “ሰው ባገሩ፣ ሰው በወንዙ
ቢበላ ሣር፣ ቢበላ መቅመቆ
ይከበር የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ” የተባለለትን፤ ከዚህ በፊት ያላየሁትን መቅመቆ አየሁ፡፡ “ገጠር ውስጥ ቅቤ ያነጥሩበታል፡፡” ኤሌፋንት ግራስ (ዝሆኔ) አለ፡፡ “የደብረ ብርሃን ተክል አደለም፡፡ የቆላ ወይም የወይና ደጋ ነው፡፡ ሆኖም እዚህ በቅሏል፡፡ አየሩ መለወጡን ያሳያል” አሉኝ፡፡
“ልዩ ልዩ ትምህርትና ሥልጠና እንሰጣለን” አለኝ የከተማ ግብርና ኑሮ ማሻሻያ ሴክሺን ኦፊሰር ቴድሮስ ቡታ፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አየን፡፡ ዘመናዊ የወተት ልማት አለ፡፡ ለህዝቡ ሥልጠና ይሰጥበታል፡፡ ልት የሚባል ለፀጉር መታጠቢያ የሚያገለግል ተክልም አለ፡፡
የሠርቶ ማሳያ ሞዴሉን እርሻ ጐብኝቼ የእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅትን ድንቅ ጥረት በደብረብርሃን አድንቄ ቀጣዩን የድሬዳዋ ጉዞዬን ላደርግ ፊቴን ወደዚያው አዞርኩ፡፡ እግረ መንገዴን በደብረ ብርሃን እጅግ የሚታወቀውን አዳራሽ የአረቄ መሸጫና መጠጫ እልፍኝ አየሁ፡፡ አንድ ሰው እንዲያስረዱኝ ጠየኩ “የደብረ ብርሃን ሰው የደብረ ብርሃንን ብርድ እንዴት እንደሚቋቋመው ያቃል” አሉኝ፡፡
                                           * * *
የድሬዳዋ ጉዞዬ
“አደጋ ባህል ከሆነን፣ እስኪ እግዚሃር ይመስገና
ይኸው ለዓመት ጉድ በቃ!”
ፀጋዬ ገ/መድህን “እንኳን ለዓመት ጉድ አበቃን” ለሚለው ያልታተመ ግጥሙ እንደ አዝማች የተጠቀመበት የግጥም መሥመር ነው፡፡ ግጥሙ ያነጣጠረው፣ አንድ ጊዜ ፍልውሃ አካባቢ በጐርፍ ተጥለቅልቆ ሰውም፣ መኪናም፣ ንብረትም የተወሰደ ጊዜ መዘጋጃ ቤት ቅድመ ዝግጅት እንዴት አያደርግም ለማለት ነበር፡፡ ስለ ድሬዳዋ ጐርፍ ላነሳላችሁ ነው የፀጋዬን ግጥም መጥቀሴ፡፡
አቤ የእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት(ጄክዶ) የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሲሆን፤ ወዳጄ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ስለድሬዳዋ ጉዞዬ ስፅፍ አንስቼላችሁ ነበር፡፡
ዛሬ ማምሻዬን ከሱ ጋር ነው ቆይታዬ፡፡ አንድ ቡና ቤት ደጃፍ ወንበር አስፋልቱ ድረስ ወጥቶ አግኝተን ተቀምጠን ሻይ ቡና እያልን ነው የምንወያየው፡፡ ነፋሻው የድሬዳዋ አየር በጣም ደስ ይላል፡፡ የቀኑ ቃጠሎ ለማታው ነፋሻ አየር ቦታውን ለቅቆ እሹሩሩ እያለን ነው፡፡
በእኔና በአቤ ጨዋታ ነፋሻው አየርም ተመስጦ “ምነው እነዚህ ሰዎች እስኪነጋ በቆዩልኝ?” ሳይል አልቀረም፡፡
ማታ መኝታዬ ላይ አመሻሻችንን ማስታወሻዬ ላይ እያሳረፍኩ፤ ላስታውሰው ሞከርኩ፡፡
ብዙ ነገር ተጫውተናል፡፡ “የወጌሻ በቅሎ በተኩስ ታልቃለች” የሚለው ተረቱ በተለይ ማርኮኛል፡፡ ወጌሻ በቅሎው በቆሰለች ቁጥር ይተኩሳታል፡፡ እንዲሁ እንደተተኮሰች ትሞታለች፡፡ (አበበ መኰንን) አቤ ጨዋታ ይችላል፡፡ ጨዋታውን ለእኔ በሚጥመኝ ቋንቋ መናገሩ፤ ከሁሉም በላይ ልዩ ያደርገዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰው ብዙ አይገኝም፡፡ በጨዋታው ውስጥ ቁም ነገር የሚያኖርና ቁምነገሩን በለዛ የሚያቀርብ በጣም ጥቂት ሰው ነው ያለው፡፡ በዚያ ላይ አቤ በጣም በጣም በጣም ሥራውን ያቀዋል፡፡ ማህበረሰቡን እንደ እጁ መዳፍ መስመሮች ያቀዋል፡፡ የሥራው ብልት የትጋ እንደሆነ ስለሚያቅም ስለሥራው ሲጠየቅ እንደሰላምታ ነው የሚመልሰው፡፡ እንዲህ ያለም ሰው ብዙ አይገኝም፡፡ እንደተፈጥሮው ያህል ተዋህዶታል፡፡ አቤ ድሬዳዋን ራሷን ነው፤ እላለሁ አንዳንዴ በሆዴ መሠረቱ ባሌ አርሲ ነው፡፡ ሥራውን እንዴት እንደሚሠራና፣ ከሥራው ጋር አንድ አካል አንድ አምሳል የመሆኑን ነገር ሲያጫውተኝ ውስጡ ትልቅ ትምህርት አገኝበታለሁ፡፡
የውይይታችን አንዱ ቁም ነገር፤
“ብዙዎቻችን ያተኮርንበትን ነገር ከሚገባው በላይ ለማሳካት ባለን ውጥን የግል ህይወታችን እየከሳ እየከሳ እየመነመነ፤ ሲነግሩን ሳንሰማ፣ ሲመክሩን እንቢ ስንል፤ እንዲሁ ጊዜያችንን እናባክነዋለን፡፡ አልሠራንም ማለት አይደለም እንሠራለን” ይላል አቤ፡፡ “አዎ ነገሩ የሚገባን፣ ድንገት ብንታመም የምንሠራበት ድርጅት ሁለት ሦስት ወር አብሮን ይቆይ ይሆናል፤ ገንዘብ እያወጣ እያሳከመን እያስታመመ፡፡ እጅግ አሰቃቂው ሰዓት ሲደርስ ግን በሚስትና ልጆች ላይ ትወድቃለህ፡፡ ይሄ ደግሞ “ለምንድን ነው የለፋሁት እስከዛሬ” የሚል ኀይለኛ ፀፀት ይፈጥራል፡፡ ስንሠራ ኖረን ተፀጽተን እንድንሞት መሆን ደግሞ ደግ አደለም፡፡ ስለዚህ ሚዛን የስፈልጋል፡፡ ለድርጅትህ መስጠት ያለብህን ሳትነፍግ፤ ቤተሰብህንም አለመርሳት አለበህ፤” አልኩት፡፡
ጠዋት አቤ ወደሥራ ቦታ ሊወስደኝ መጣ፡፡ “ተነስተሃል?” አለኝ፡፡ “ኧረ አንድ የሚገርም መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ የMichela Wrong” ን “I Didn’t Do It for you”፡፡ እዚያ ላይ ምን ገረመኝ መሰለህ?
ደራሲዋ ግብጽ ኤርፖርት ያገኘችው አንድ መንገደኛ ፓኪስታናዊ እንዲህ ሲል ይጠይቃታል፡፡
“አንቺስ ምን እየሠራሽ ነው?”
“ጋዜጠኛ ነኝ፡፡ ስለ ኤርትራ መጽሐፍ እየፃፍኩ ነው፡፡ አሁን የምሄደውም ወደዚያ ነው” ትለዋለች፡፡
ሽፋሽፍቶቹን ስብስብ አድርጐ፣ በትክክል አልሰማኋትም በሚል ስሜት፤
“ስለ አልጄሪያ መጽሐፍ እየፃፍሽ?” አላት፡፡
“አይ ስለአልጄሪያ አይደለም፤ ስለ ኤርትራ”
“አሃ ስለናይጄሪያ?” አሁን በሃሳብ እየባዘነ ነው፡፡
“አይደለም” አለችው፡፡
አሁን ጭራሹን ገደል የገባ ግምት ገመተ:- “ስለ አልጀዚራ??”
ከአቤ ጋር ተሳሳቅን፡፡
“ወደ አንድ ማህበር ነው የምንሄደው፡፡ አየህ እያንዳንዷ ትናንሽ ማኅበር ከማህበረሰቡ ትወጣና ሰፍታ ትልቅ አገር ትፈጥራለች፡፡ አንዷ ክር ትመዘዝና ክሯ ተገጣጥማ መረብ ትሆናለች…
ወደ “በድሬዳዋ አስተዳደር ማህበረሰብ መር የአደጋ ሥጋት ቅነሳ የበጐ አድራጐት ማኅበር” ነው የምንሄደው፡፡”
የማኅበሩን ሰብሳቢ አስተዋውቆኝ አቤ ሄደ፡፡ እሳቸውና እኔ ውይይት ቀጠልን፡፡
“እኔ ሻለቃ አየለ ካሤ እባላለሁ፡፡ ማኅበራችን ታሪካዊ አመጣጡ… ድሬዳዋ ብዙ ህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው በጐርፍ የሚጠቁት፡፡ በአራት ሳይቶች ነው አደረጃጀቱ 4 Village ኮሚቴዎች አሉት፡፡ ቦርድ 7 አባላት አሉ፡፡ 4ቱ ከማህበረሰቡ 3ቱ ከውጪ ከሴክተሮች የመጡ፡፡ 1 ዓመት ነው የሠራ ነው፡፡ የጄክዶ አደረጃጀት ከተፈጠረ በኋላ፤ ነው ይሄ ሁሉ፡፡
ከታሪክ እንደምንረዳው ከ1937 ዓ.ም ጀምሮ ነው የጐርፍ ጥቃቱ፡፡ 1973-75 እኛ የምናውቀው ያየነው ነው፡፡ ይህም ፈረቃው በ10 ዓመት፣ በ6 ዓመት፣ በ2 ዓመት እያለ ይከታተል ጀመር፡፡ በየ6 ወሩ እየመጣ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስ ነበር፡፡ ህዝቡ ፈጣሪያችን ያመጣብን ነው ብሎ የመቀመጥ ኋላቀር አስተሳሰብ ነበረው፡፡ እሱ ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው የሚል ሃሳብ ነበረው፡፡ እየባሰ እየባሰ ሲሄድ ደግሞ “መንግሥት ለምን አይከላከልልንም?” “ለምን ዝም ይለናል ስናልቅ ስንፈናቀል”፤ ይል ጀመር፡፡ 1998 ዓ.ም ላይ እጅግ የከፋ ሆነ! ከደጋው የዘነበው ዝናብ ባጭር ጊዜ ተንደርድሮ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ ፌዴ/መንግሥቱን ያንቀሳቀሰና ጠ/ሚኒስትሩ ጭምር በቦታው ተገኝተው እንዲያዩት ያስገደደ ነው፡፡ የዓለም አቀፉን ሚዲያም የሳበ ነው! ማህበረሰቡም ራሱን መጠየቅ ጀመረ፡፡ መለወጥ ጀመሩ ገንዳ አዳና ኮካ በደቡብ ወገን ያሉት በጣም ተጠቂ ነበሩ፡፡ በምዕራብ ደሞ አርጌሌ፣ ጂቲ ዜድ፣ መርመረሣ እያለ ቀጠለ፡፡ ድሬዳዋ በድንጋይ የተከበበች ናት፡፡ በ1 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ተምዘግዝጐ ደረሰ - አጥለቀለቀው!! ያ ጉዳት ሐምሌ 29 ቀን ከሌሊቱ 9 ሰዓት ነው! እጅግ አስከፊ ነበር!!
ህብረተሰቡ መፍትሔ አሻ፡፡ “እንዴት እንከላከል?” ማለት መጣ፡፡ የኢየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (የኢህማልድ) እዚህ ጋ ይመጣል፡፡
ቀደም ብሎ በአካባቢው ላይ ይሠራ ነበረ፡፡ በተወካዮች አማካኝነት ለሱ ጥያቄ ቀረበ፡፡ ኢህማልድ (ጄክዶ) ጥያቄውን በአንክሮ ተቀብሎ በአካባቢው ላይ ጥናት ተጀመረ፡፡ ማህበረተሰቡ ውይይት ጀመረ፡፡ ለሣይቶቹ 200 ሰዎች (800) ለነሱ የawareness (የግንዛቤ ማስጨበጥ) ሥራ ተሠራ፡፡ የመንደር ኮሚቴዎች ተፈጠሩ፡፡
ይቀጥላል

Published in ህብረተሰብ

በአስረስ አሰፋ ተፅፎ በድንቅስራው ደረጄ እና ያሬድ መንግስቴ የተዘጋጀው “የእኔ እውነት” የተሰኘ ትያትር ከህዳር 14 ጀምሮ በዓለም ሲኒማ ለተመልካች እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡ ትያትሩ ከአንድ አመት በላይ ተደክሞበታል ያሉት አዘጋጆቹ፤ ዘወትር ቅዳሜ ከቀኑ 10 ሰዓት እንደሚታይም አስታውቀዋል፡፡ የትያትሩ ደራሲና ፕሮዱዩሰር አለም ሲኒማን የመረጡትን በመንግስት ትያትር ቤቶች ወረፋው አታካች በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ “ዓለም ሲኒማ ቀና ትብብር አድርገው ወዲያው ነው የፈቀዱልን፤ በቦሌ መንገድ ግንባታ ምክንያት ዘገየ እንጂ አምና ነበር የሚከፈተው” ሲሉም አክለዋል፡፡
በትያትሩ ላይ በ“ሰው ለሰው” የቴሌቪዥን ድራማ የምትሰራውን አርቲስት ምስራቅ ወርቁን ጨምሮ ተዘራ ለማ፣ ዳዊት ፍቅሬ፣ ጥሩዬ ተስፋዬ፣ ቢኒያም ፍቅሩ፣ አስረስ አሰፋ፣ ፍቅሩ ባርኮ እና እምነት ከፈለ ተውነውበታል፡፡

Page 8 of 19