የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ጥበባት ት/ቤት የመጀመሪያ የሆነውን ዓመታዊ የትያትር ፌስቲቫል እንደከፈተ ተገለፀ፡፡ ትናንት በዋናው ግቢ የባህል ማዕከል ፋውንቴን እና አምስት ኪሎ በሚገኘው የድህረ - ምረቃ አዳራሽ የተከፈተው ፌስቲቫል፤ ለዘጠኝ ቀናት ክፍት ሆኖ  እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ዘጠኝ የት/ቤት ቴአትሮች ለእይታ የሚበቁ ሲሆን በሀገራችን ቴአትር አይነተኛ ሚና የተጫወቱ ስምንት ባለሙያዎች ይታወሳሉም ተብሏል፡፡
ፌስቲቫሉን በርካታ ሰዎች እንደሚጐበኙት ይጠበቃል፡፡

Saturday, 08 November 2014 11:29

የቀልድ ጥግ

ጋዜጠኛው ወደ ኢትዮጵያ ለስራ የመጣ አንድ ቻይናዊ እያነጋገረ ነው፡፡
ጋዜጠኛ - ቻይና ውስጥ አንድ አምፑል ለመቀየር ስንት ቻይናውያን ያስፈልጋሉ?
ቻይናዊ - አንድ በቂ ነው፡፡
ጋዜጠኛ - ኢትዮጵያ ውስጥስ አንድ አምፑል ለመቀየር ስንት አበሾች ያስፈልጋሉ?
ቻይናዊ - አምስት፡፡ አንዱ አምፑል ለመቀየር፣ አንዱ ወንበር ለመያዝ፣ ሶስቱ ደግሞ   ቆመው ለመመልከት፡፡
ጋዜጠኛ - ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አምፑል ለመቀየር ስንት ቻይናውያን ያስፈልጋሉ?
ቻይናዊ - አምስት፡፡ አንዱ አምፑል ለመቀየር፣ አራቱ ቆመው የሚመለከቱትን አበሾች  ለማባረር፡፡
ጋዜጠኛ - ቻይና ውስጥ አንድ አምፑል ለመቀየር ስንት አበሻ ያስፈልጋል?
ቻይናዊ - አንድ አበሻና ሶስት ቻይናውያን፡፡
አበሻው አምፑሉን ለመቀየር፣ ሶስቱ ቻይናውያን ደግሞ ሃበሻው አምፑሉን ቀይሮ ሲጨርስ አገሬ አልመለስም  
   እንዳይል ለመጠበቅ፡፡

Published in ጥበብ

እንዳለመታደል ሆኖ “የራሳችን ነገር ያንስብናል” መሰል የእኛ ስለሆነው ነገር ከመናገር ይልቅ ስለ ሌሎች ማውራትና በሌሎች መርካት እንመርጣለን፡
እናም ማንነታችንን በቅጡ የሚገልጸው ሀብታችን ሁሉ “ባለቤቱ ያቀለለው አሞሌ” ሆኖና ተረስቶ ተረት ለመሆን እየተንደረደረ ይመስላል- “ነበር” ለመባል፡፡
የዛሬው ጽሑፌ ጉዳይ እጅጉን እውቅና እና ትኩረት ስለተነፈገው ኢትዮጵያዊው የአንድምታ ትርጓሜ ስልት ነው፡፡ በዚህም ስለ ስልቱ ምን አይነትነትና አጀማመር እንዲሁም በሀገራችን የጽሕፈትና የፍልስፍና ታሪክ ውስጥ ስለነበረው አገልግሎትና ቦታ (ስላለውም ጭምር) ስልቱን ሊያስተዋውቅ በሚችል መልኩ በጥቂቱ አወሳለሁ፡፡ ሆኖም እሱን ከመጥለቄ በፊት ጭራውን መያዝ እንችል ዘንድ አንድምታ ትርጓሜን ስላሰለጠነው የግዕዝ ቋንቋ ጥቂት ልበል፡፡
የግዕዝ ቋንቋን የትመጥነት አስመልከተው በርካታ መላምቶች ከቋንቋ ጥናት ሊቃውንት አንደበት ይሰማሉ፡፡ ከፊሎቹ “እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ በገነት ሲያኖረው መግባቢያ ይሆነው ዘንድ የሰጠው ነው” ሲሉ ከፊሎቹ ደግሞ “የአዳም የልጅ ልጆች በጊዜ ሂደት ለመግባቢያነት የፈጠሩት ነው” ይላሉ፡፡ ከነዚህ በተለየ የቋንቋን አፈጣጠርና ስርጭት እንዲሁም መዋለድን መላምቶች አጣቅሰው “ግዕዝ ቋንቋ የተገኘው እንዲህ ነው” የሚሉ ወገኖችም አሉ፡
የግዕዝ ቋንቋ ቀደም (በተለይ ከ11ኛው ክፍለ ዘመን አስቀድሞ በነበሩት ተከታታይ አራት ምዕቶች) በኢትዮጵያ በነበረው አገልግሎት ላይም እንዲሁ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡

አንዳንዶች “ቋንቋው ለመላው የአቢሲንያ ህዝብ የአፍ መፍቻና ብሔራዊ ቋንቋ ነበር” ሲሉ ሌሎች ደግሞ የለም “በሰሜን ኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩት ህዝቦች ብቻ መግባቢያ ነው የነበረው” በማለት ሁለቱም አካላት አለን የሚሏቸውን ማስረጃዎች በመጥቀስ ይሞግታሉ፡፡ የት መጥነቱና በቀደመው ዘመን የነበረው አገልግሎት ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶችን ለጊዜው  ትተን (ጉዳዩ በጋዜጣ አምድ የሚቋጭ ባለመሆኑ) የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን በብዙ ያጠኑ የቋንቋ ሊቃውንት ግዕዝን በተመለከተ የሚስማሙባቸውን እውነታዎች እንጠቃቅስ፡፡
የግዕዝ ቋንቋ በሴም የቋንቋ ቤተሰብ ስር የሚመደቡትን ትግረን፣ ትግርኛንና አማርኛን ወልዶአል፡፡ ቋንቋው የራሳቸው የሆነ መሰረትና የጽሕፈት ባህል ካላቸው ቋንቋዎች አንዱ በመሆኑም በርካታ የሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የሕግ፣ የፍልስፍና፣ የሂሳብ ወዘተ መጻሕፍት ተጽፈውበታል፡፡ ተተርጉመውበታልም፡፡ በቋንቋው ያልተበጀ ስነ ጽሑፋዊ ዘር አናገኝም፡፡ ግጥም፣ ልቦለድ፣ ስነቃል፣ የሕይወት ታሪክ፣ ትርጉምና ትንታኔዎች… በግዕዝ ተበጅተዋል፡፡ ቀዳሚያኑ ነገሥታት ከአውሮፓ አቻዎቻቸው ጋር የደብዳቤ ልውውጥን ለማድረግ ግዕዝን ተገልግለዋል፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ይህን የመሳሰሉ ክንውኖችና ዕውቀቶች የተሰሩበት፣ የተራቀቁበትና የተስፋፉበት ግዕዝ ከፈጠራቸው ዕውቀቶች አንዱ የአንድምታ ትርጓሜ ስልት ነው፡፡ ይህን ታላቅ ዕውቀት አርቅቀውና አምጥቀው ያቀበሉንን ሊቃውንት እጅ ነስተን ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡
አንድምታ የትርጉም ስልት ወይም መንገድ ነው፡፡ በአንድምታ መተርጎም ማለትም አንድን ቃል በብዙ መፍታት ወይም የተለያየ ትርጓሜ (Interpretation) መስጠት፣ ዋናውን ምስጢር “አስፍቶና አምልቶ” ማሳየት ሲሆን በዚህም በገጸ ንባቡ (Text) ፊት ለፊት የተባለውንም ሆነ የተደበቀውን ሀሳብ ማሳየት ነው፡፡
አንድምታ ትርጓሜ መቼና የት ተጀመረ? ለሚለው ጥያቄ እስከ አሁን እርግጠኛ የሆነ መልስ መስጠት የተቻለ አይመስልም፡፡ ያም ሆኖ ግን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በአይሁድ ሊቃናት አማካይነት የተሰሩና ታልሙድ (Talmud) በመባል የሚታወቁ “የትርጉም” መጻሕፍት እንደነበሩ የታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዛም በኋላ “ትርጓሜ” በዘመነ ሀዲስ በክርስቶስ ሲተገበር እንደነበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት  ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ወንጌልን በተለያየ ምሳሌ ማስተማሩን፣ ምሳሌውንም ለደቀ መዛሙርቱ እየተነተነ ማስረዳቱን በአስረጂነት ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ማስረጃ በራሱ የሚመልሰው ነገር ቢኖርም “ክርስቶስ ምሳሌዎቹን ተንትኖ ያስረዳበት መንገድ ከአንድምታ ትርጓሜ ስልት ጋር ተመሳሳይ ነው ወይ?” ከሚል ጥያቄ ግን የሚያመልጥ አይደለም፡፡
ቆይቶም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተለይ በአራተኛው ክፍለ ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን፣ ለዚህም በዘመኑ ገናና በነበሩት ሁለት ታላላቅ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች አንጾኪያ(ሶርያ) እና እስክንድርያ(ግብፅ) ሊቃውንት አማካይነት ታላላቅ መጻሕፍት መተርጎማቸው ይነገራል፡፡
ለዚህ ምክንያት የነበረው “ሰዎች የመጻሕፍትን የላይ ንባብ ብቻ በመያዝና ጠልቀው ባለመረዳት ለክህደት በመዳረጋቸው፣ ለብዙዎችም መሳት ምክንያት እየሆኑ በመምጣታቸው” መሆኑ መስኩን ያጠኑ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ይህንን ችግር ለመፍታት መጻሕፍትን ከላይ አርዕስታቸውን ከታች ህዳጋቸውን በመመልከት አንዱን በአንዱ በመመርመር፣ በማመዛዘንና ጠልቆ በመረዳት እነ ዮሐንስ አፈወርቅ ፣ ቄርሎስ፣ ቴዎፍሎስ በጠቅላላው በሃይማኖተ አበው (በዘመነ አበው) የነበሩ ሊቃውንት ቅዱሳት መጻሕፍትን በሰፊው ተርጉመዋል፡፡ በወቅቱም ትርጓሜ በምስጢረ ሥላሴ፣ ምስጢረ ሥጋዌና በጠቅላላው በስነ መለኮት ላይ ለተነሱ የሀሳብና የአመለካከት ልዩነቶች ጠንካራ መልስ ለመስጠት አስችሎአል፡፡
ቅድመ ልደተ ክርስቶስም ሆነ ድህረ ልደተ ክርስቶስ የነበረው የትርጓሜ ስልት በኢትዮጵያ ለአለው የአንድምታ ትርጓሜ ስልት “መነሻ ሆኖአል” ብንልም የኢትዮጵያው ስልት ከቀዳሚዎቹ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የአንድምታ ትርጓሜ፣ በትርጉም ስልት ውስጥ ከተለመደው ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ ከሚደረግ የቃል በቃል ትርጉም ወይንም በአንድ ቋንቋ ውስጥ ከሚካሄድ የማብራሪያ ትርጉም መለየቱን ልብ እንበል፡፡
የአንድምታ ትርጓሜ በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ስለአንድ ጉዳይ የተለያዩና እርስ በእርስ የሚጋጩ በሚመስሉ ሀሳቦች ላይ አንዳች አሳማኝና ማጠየቂያ የሚቀርብበት ፍቺ ለመስጠት የሚደረግ ስልት መሆኑ ከላይ ከጠቀስናቸው ሁለት የስነ መለኮት ትምህርት ቤቶች የትርጉም መንገድ ጋር የሚያመሳስለው ቢሆንም ልዩነቱ የጎላ ነው፡፡ የአንድምታ ትርጓሜ ምንም እንኳን የግዕዝ መጻሕፍትን ወደ አማርኛ ቋንቋ ቢተረጉምም ዋናው ጉዳዩ ግን እሱ አይደለም፡፡ የገጸ ንባቡን ፍቺ ከዘይቤ ፍቺ (የላይ ትርጉም) አላቆ ምስጢሩን ማውጣትና ማስረዳት ነው፡፡ ይህንንም ሲያደርግ አስረጂዎችን በሁለቱም ቋንቋዎች ያመጣል፡፡ እንዲሁም የሚጋጩ የሚመስሉ ሀሳቦችን አመሳክሮ ለማስታረቅ፣ ለማስረዳትና ምስጢሩን ለማስጨበጥ እጅግ በርካታ ማጠየቂያዎችን ከገጸ ንባቡ (Text) ወጥቶ ከታሪክ፣ ከፍልስፍና፣ ከሕግ… ያመጣል፡፡ በዚህም እንዲህ ሲል እንዲህ ማለቱ ነው፡፡ አንድም እንዲህ ሲል ነው፡፡ አንድም እንዲህ ነው… እያለ ለአንድ ቃል፣ ሐረግ ወይም አረፍተ ነገር እጅግ በርካታ ፍቺዎችን በማዝመር የተበተነና አደናጋሪ የሚመስለውን ሀሳብ ያስራል፡፡ ያስረዳልም፡፡
የአንድምታ ትርጓሜ በኢትዮጵያ በዚህ ጊዜና ቦታ ነው የተጀመረው ለማለት በቂ መረጃ ባይኖርም ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ፋሲል ዘመነ መንግስት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና በአጠቃላይ እንቅስቃሴዋ ከፍተኛ በነበረችው ጎንደር እንደተስፋፋ ይስማማሉ፡፡ ከዚህ ቀድሞ አባ መዝሙረ ክርስቶስ የተባሉ ጎጃም ሞጣ ላይ የነበሩ መነኩሴ ግብፅ ሀገር ሄደው አረብኛ ቋንቋን በመማር፣ በግብጾች በአረብኛ ቋንቋ ተጽፎ የነበረውን የአንድምታ ትርጉም ወደ ግእዝ ቋንቋ እንደተረጎሙ፣ መጽሐፉም በአሁኑ ጊዜ ሞጣ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ይህ የቃል በቃል የቋንቋ ትርጉም እንጂ የአንድምታ ትርጉሙ በኢትዮጵያ ሊቃውንት፣ በኢትዮጵያ… የተጻፈ ባለመሆኑ አንድምታ ትርጓሜ በኢትዮጵያ በዚህ ሥራ ነው የተጀመረው ለማለት አይቻልም፡፡
በወቅቱ ጎንደር የንጉሡ መቀመጫ ከተማና የትምህርት ማዕከል በመሆኗ የብዙ ሊቃውንት መሰብሰቢያ ነበረች፡፡ እኒህ ሊቃውንትም በመሰባሰብ ቅዱሳት መጻሕፍትን መተርጎምና ማብራራት ጀምረዋል፡፡ የትኛው መጽሐፍ ቀድሞ እንደተተረጎመ የሚገልጽ መረጃ ባይኖርም ብዙ የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህራን ግን ሀዲስ ኪዳን (በተለይም አራቱ ወንጌላት) ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ሆኖም አሁንም ዘመኑን በትክክል መናገር ባይቻልም (ከጎንደር በኋላ) በጎጃም ሞጣ የነበሩ አቶ አደራ የተባሉ ሊቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሉያትን ሰብስበው ያጠኑና ይተረጉሙ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከዚያ በፊት ብሉያትም ሆኑ ሌሎች መጻሕፍት የሚጠኑት በተናጠል ነበር፡፡ በጎንደር የጎመራው የአንድምታ ትርጓሜ ትምህርት እዚያው ጎንደር ሐመረ ኖህ፣ በመቀጠልም በሐይቅ እስጢፋኖስ፣ በጎጃም ሞጣ እንዲሁም በዲማ፣ በወሎ ተድባበ ማርያም ተስፋፍቶአል፡፡ እነዚህ ቦታዎች ከጥንት ጀምሮ ታላላቅ የአንድምታ ትርጓሜ ትምህርት ቤቶች የነበሩባቸው ሲሆን እስከ አሁንም ድረስ ብዙ ሰዎች ይህንን ዕውቀት ለማግኘት የሚጓዙባቸው ናቸው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ እየተስፋፋና እያደገ የመጣው የትርጓሜ ትምህርት የሙያው ጠቃሚነትና ተከባሪነት እያየለ በመምጣቱ፣ ትምህርት ቤቶች በሀገሪቱ አልፎ አልፎም ቢሆን እንዲተከሉ አድርጎአል፡፡ በአንድምታ ትርጓሜ ሙያ በየዘመናቱ ታላላቅ ሊቃውንትና መምህራን ተነስተዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም መምህራኖቻቸውን እየተኩና ዕውቀቱም እየተወራረሰ ኖሮአል፡፡ ከቀደሙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መካከል ቀጥለው የተጠቀሱት ጎልተው ከወጡትና “የአንድምታ ትርጓሜ አይን” ከሚባሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
መ/ር ኤስድሮስ፣ መ/ር ስነ ክርስቶሰ፣ አቃቤ ሰዓት ከብቴ፣ መ/ር ወልደ አብ፣ አቶ አየለ፣ አራት አይና ጎሹ፣ መ/ር አካለ ወልድ፣ አቡነ አብርሐም፣ ዶ/ር አየለ፣ ሊቀ ሊቃውንት መንክር እንዲሁም መልዐከ ገነት ገ/ሥላሴ ተጠቃሾች ናቸው፡፡የቀደሙ አባቶች ሊቃውንት፤ ብራና ፍቀውና አለዝበው፣ ቀለም በጥብጠው፣ መጻሕፍትን በመተርጎም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለዓለም አበርክተዋል፡፡  የአንድምታ ትርጓሜ ስልት ጥቅሙ የጎላና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምጥቃና ጠብቃ ካቆየቻቸው የሀገራችን ባህላዊ ዕውቀቶች አንዱ ነው፡፡ ዕውቀቱም በቤተ ክርስቲያኒቷ ትምህርቶች ውስጥ ትልቅ ቦታና ክብር አለው፡፡
የአንድምታ ትርጓሜ የአተረጋጎም ስልቱ/መንገዱ ብዙ ቢሆንም በአብዛኛው አገልግሎት ላይ የሚውሉት የሚከተሉት ስልቶች ናቸው፡፡ እነዚህም ዘይቤ፣ የዘይቤ አወጣጥ፣ የዘይቤ ፀያፍ ማቅናት፣ ግጥም፣ አወራረድ፣ አርዕስት አይቶ መተርጎም፣ ውጥን ጨራሽ፣ አንጻር፣ ማስማማት፣ ሐተታ፣ ታሪክ፣ ዕርቅ እና ምስጢር ናቸው፡፡ ይህን ያህል ታላቅና በርካቶች ሊካኑበት የሚገባው የአንድምታ ትርጓሜ ዕውቀት አሁን ያለበትን ደረጃ መናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ ቀድሞውኑም ደክማ ያበለጸገችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያለአጋዥ አሁንም ለትውልድ ለማስተላለፍ ብቻዋን ትንገታገታለች፡፡ የማስተማሪያ ስልቱም እጅጉን አድካሚ ከሆነው ባህላዊ መንገድ አሁንም አልተላቀቀም፡፡ የትርጓሜን ትምህርት ከመምህራኑ ቃል በቃል ተቀብሎ ከማጥናት በቀር በጽሑፍ ማስፈር አይታወቅም፡፡ ይህም በመምህራኑም ሆነ በተማሪዎቹ ላይ የኑሮ ጉዳት አድርሶአል፡፡ እያደረሰም ነው፡፡ የዕውቀቱ መተላለፊያ መንገድ ከጽሑፍ ይልቅ በቃል መሆኑም መምህራኑ ዕውቀታቸውን ለተከታዮቻቸው ሳያስተላልፉ ይዘውት ወደ መቃብር እንዲወርዱ አድርጎአል፡፡ የአንድምታ ትርጓሜ (የአተረጓጎምና የአረዳድ ስልቱ) በዘመናዊው የትምህርት ስርዓት ውስጥ ሊካተትና እንደአስፈላጊነቱ ሊተገበር የሚገባ ቢሆንም የእኔ ነው የሚለው እና እውቅና የሰጠው የለም፡፡ ያም ቀርቶበት ባለበት ሁኔታ ለመቆየትም ብዙ ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ ዕውቀቱ ለዘመናት የሙጥኝ ባለው አድካሚ የማስተማሪያ ስልትና ትምህርት ቤቶቹም ሆኑ መምህራኑ በቂ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሟል፡፡
ለአንድምታ ትርጓሜ አለማደግ (ይልቁንም መዳከም) በርካታ አካላትን “ተወቃሽ” ማድረግ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዕውቀቱን ጠብቃ ስታስተላለፍ መኖሯ የሚያስመሰግናት ቢሆንም የትምህርት ስልቱን ለማዘመንም ሆነ ዕውቀቱን  ለማስተዋወቅ ጥረት አላደረገችም፡፡ የትምህርትና የፍልስፍና የጥናት ዘርፎችና ባለሙያዎቻቸውም የራስ የሆነን ዕውቀት ፈልጎ ከማውጣት፣ አውጥቶም ከማዘመንና ከማሳደግ ይልቅ በምዕራባውያን ፍልስፍና እና ዕውቀት ተጠምደዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችንም እንዲሁ፡፡ እናም እኛ የእኛ ስለሆነው ነገር ከምናውቀው በላይ የውጪ ዜጎች የእኛ ስለሆነው ብዙ ያውቃሉ፡፡ እኛም ድከሙ ብሎን በምላሳችን ልክ የተሰራልንን አሞሌያችንን አቅለን በሌሎች ምላስ ልክ የተሰራውን አሞሌ እንልሳለን፡፡
መልካም ሰንበት!!   

Published in ጥበብ

ስልጣኑን ካላስረከበ አገሪቱን ከህብረቱ አባልነት አግዳለሁ ብሏል
ፓርቲዎች እስከ 1 አመት የመንግስት ሽግግር ለማድረግ ተስማምተዋል

            ቡርኪናፋሶን ለ27 አመታት የመሩት ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ በህዝብ አመፅ ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ የአገሪቱ የጦር ሃይል ስልጣን የያዘበት አካሄድ ህገ መንግስታዊ ስርዓትን የተከተለ አይደለም ሲል የተቃወመው የአፍሪካ ህብረት፤ ጦሩ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ለሲቪል መንግስት ስልጣን እንዲያስረክብ ቀነ ገደብ ማስቀመጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከንቅናቄ መሪዎች ጋር ውይይት ያደረጉት የአገሪቱ የጦር ሃይል መሪ ሌ/ኮሎኔል አይዛክ ዚዳ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ስልጣን እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ፤ ጦሩ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ስልጣኑን የማያስረክብ ከሆነ፣ ቡርኪናፋሶን ከህብረቱ አባልነት ከማገድ አንስቶ በጦር መኮንኖች ላይ የጉዞ ማዕቀብ እስከመጣል የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
ድንገት የተቀሰቀሰው የቡርኪናፋሶ ህዝባዊ አመጽ ብሌስ ኮምፓዎሬን ከስልጣን ማውረዱን ተከትሎ፣ አገሪቱን የማስተዳደሩን ስልጣን የተረከበው የጦር ሃይል በአፋጣኝ ስልጣኑን ለተገቢው መሪ እንዲያስረክብ ሁኔታዎችን የማመቻቸት አላማ የያዘው የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች የልኡካን ቡድን፣ ወደ አገሪቱ በማምራት በጉዳዩ ዙሪያ መምከሩን ዘገባው ገልጿል፡፡
ጦሩ ስልጣኑን በአፋጣኝ እንዲያስረክብ ለማግባባት ወደ ቡርኪናፋሶ ያመሩት የጋና፣ የናይጀሪያና የሴኔጋል መሪዎች ከትናንት በስቲያ ከጦር ሃይሉ መኮንኖች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ አካላት፣ ከጎሳ መሪዎችና ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር መወያየታቸውንና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመጪው አመት ህዳር ወር ላይ እስከሚካሄድ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክር ቤትም በወሩ መጨረሻ በሚጠራው ስብሰባ አገሪቱን ከቀውስ ለማዳን በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ እንደሚመክርም ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡
ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ፤ ህገመንግስቱን በማሻሻል ያለ አግባብ በቀጣዩ የአገሪቱ ምርጫ ለመወዳደር መሞከራቸውን ተከትሎ፣ ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ በተቀሰቀሰው የህዝብ ተቃውሞ ከስልጣን መውረዳቸው ይታወሳል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

615 ሚ. ዶላር ወጥቶበታል፤ ተጨማሪ 85 ሚ. ፓውንድ ለማስፋፊያ ተመድቦለታል
ለፕሬዚዳንቱ ልዩ አውሮፕላን 115 ሚ. ፓውንድ ተከፍሏል
3 ሚ. ቱርካውያን ስራ አጦች ናቸው

           የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሪሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን፤ በ615 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያሰሩትና አንካራ ውስጥ በሚገኝ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ስኩየር ጫማ ቦታ ላይ ያረፈው ግዙፉ ‘ነጩ ቤተ መንግስት’ በአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ተቃውሞ ማስነሳቱን ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ለ12 አመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያስተዳደሩትና በቅርቡ የፕሬዚዳንትነት ስልጣን የያዙት ኤርዶጋን፤ ከታዋቂዎቹ ዋይት ሃውስና ቤኪንግሃም ቤተመንግስቶች እንደሚበልጥ የተነገረለትን ይህን ቤተመንግስት ማሰራታቸው፣ በአገሪቱ ግብር ከፋይ ዜጎች ዘንድ አላግባብ ወጪ የወጣበት የቅንጦት ግንባታ በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ከሳምንታት በፊት ግንባታው ተጠናቆ ስራ የጀመረውና “አክ ሳራይ” ተብሎ የሚጠራው ቤተ መንግስት፤ በከፍተኛ ወጪ ከመገንባቱ በተጨማሪ፣ በአረንጓዴ ቦታነት በተከለለ ስፍራ ላይ መሰራቱ በአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ዘንድ ተቃውሞ እንዳስነሳ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
“ፕሬዚዳንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዛፎችን ጨፍጭፈው በከፍተኛ ወጪ የራሳቸውን የቅንጦት ቤት የገነቡት፣ 3 ሚሊዮን ዜጎቿ ስራ አጥ በሆኑባት አገር ላይ ነው” ብለዋል - “ሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ” የተባለው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ከማል ኪሊዳሮግሉ ለቴሌግራፍ ጋዜጣ በሰጡት ቃል፡፡
በአገሪቱ ቤተ መንግስት ለመገንባት ከተመደበው በጀት ከሁለት እጥፍ በላይ ገንዘብ ፈሶበታል የተባለው ቤተ መንግስቱ 1 ሺህ ክፍሎች ያሉት ሲሆን እጅግ ዘመናዊ የሆነ ጥብቅ የደህንነት መቆጣጠሪያ ሲስተም ተገጥሞለታል፡፡
 ቤተመንግስቱ እጅግ ውድ በሆኑ የግንባታ ቁሳቁሶች የተሰራ ነው ተብሏል፡፡
‘ነጩን ቤተ መንግስት’ በቀጣዩ አመት የበለጠ እንዲያምርና እንዲስፋፋ ለማድረግ ተጨማሪ 85 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት መመደቡን የጠቆመው ዘገባው፤ ለፕሬዚዳንቱ ልዩ ኤርባስ አውሮፕላን ለመግዛት 115 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት መመደቡንም ገልጿል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ ከተለያዩ የአለማችን አገራት መንግስታት የተጠቃሚዎቹን የግል መረጃዎች አሳልፎ እንዲሰጣቸው የሚያቀርቡለት ጥያቄዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አስታወቀ፡፡ከተለያዩ የአለም አገራት መንግስታት የሚቀርቡለት ተመሳሳይ ጥያቄዎች ባለፉት ስድስት ወራት በ25 በመቶ እንደጨመ በድረገጹ ላይ የገለጸው ፌስቡክ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ 34 ሺህ 946 የመረጃ ጥያቄዎች እንደቀረቡለት አስታውቋል፡፡
ድረገጹ እንዳለው፤ የተለያዩ አገራት መንግስታት በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ክትትልና ምርመራ ለማድረግ የሚያግዛቸውን መረጃዎች ለማግኘት ጥያቄ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡መንግስታት የሚያቀርቡትን መሰል ጥያቄዎች በመቃወም በተደጋጋሚ በአሜሪካ ለሚገኝ አንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ እያቀረበ እንደሚገኝ ያስታወቀው ፌስቡክ፣ ፍርድ ቤቱ የአሜሪካ መንግስት በህገወጥ መንገድ ያገኛቸውን የተጠቃሚዎቹነረ መረጃዎች እንዲያስመልስለት አቤት እያለ መሆኑንም ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ታዋቂው ድረገጽ ጎግልም፣ የተጠቃሚዎቹን መረጃዎች አሳልፈው እንዲሰጡት በተለያዩ አገራት መንግስታት የሚቀርቡለት ጥያቄዎች ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በ15 በመቶ መጨመራቸውን ባለፈው ወር ማስታወቁን ሮይተርስ አስታውሷል፡፡
መንግስታት ለወንጀል ምርመራ የሚያቀርቡለት የመረጃ ጥያቄዎች ባለፉት አምስት አመታት በ150 በመቶ እንደጨመረ ነው ጎግል ያስታወቀው፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

“በዙሪያ ከከበቡኝ ሰዎች 99 በመቶው አይሳካልህም ይሉኝ ነበር”

          ዛሬም እንደ ባለፈው ሳምንት ከCNN ያገኘሁትን የስኬት ታሪክ አካፍላችኋለሁ፡፡ የዛሬውን ባለ ታሪክ ለየት የሚያደርገው የሚያውቁት ሁሉ እንደማይሳካለት እየነገሩ ቢያጣጥሉትም በትጋትና በቁርጠኝነት እምነታቸው የተሳሳተ እንደነበር ማረጋገጥ መቻሉ ነው፡፡ ይሄም ታሪክ መቼቱ በዚህችው በአህጉራችን በአፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ ታሪኩ ለስኬት እንደሚያነቃቃችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አሞስ ዌኬሳ፤ በአገሩ በኡጋንዳ ብዙ ለውጦችን አይቷል፡፡ ዛሬ በጥረቱ ራሱን ሚሊዬነር ማድረግ የቻለው ዌኬሳ፤ በዩጋንዳ እጅግ ግዙፍና ታዋቂ ከሚባሉት የአስጐብኚ ድርጅቶች (tour operators) አንዱ የሆነውን “ግሬት ሌክ ሳፋሪስ” በባለቤትነትና በሥራ አስኪያጅነት ይመራል፡፡
ይሄ ኡጋንዳዊ የከበረው አዲስ ነገር በመፍጠር ወይም በምርት ሥራ ላይ ተሰማርቶ አይደለም፤ የአገሩን የተፈጥሮ ሃብት በማስጐብኘት ነው፡፡ ደንበኞቹን በንግስት ኤልዛቤት ፓርክ ውስጥ በዝሆን ጀርባ በማንሸራሸር ወይም ሙርቺሰን ፏፏቴ ጋ የሚገኙትን የአካባቢውን ዝንጀሮዎች ቀረብ ብለው የማየት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግና የአገሩን አስደማሚ ውበት በማስተዋወቅ ሚሊዮን ዶላሮችን እንዳካበተ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
“በግሌ መላውን ዓለም ተጉዣለሁ፤ በዚህ ሥራ ተጠቀምኩ ከምላቸው ነገሮች መካከል በአስጐብኚነት የራሴን አገር ተዟዙሬ ማየቴና ቱሪስቶች በአካባቢው ውበት ምን ያህል እንደሚደመሙ ለመታዘብ መቻሌ ነው” ይላል ዌኬሳ፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ቢመጣም ሁሌም ግን እንዲህ አልነበረም፡፡ ባለፈው ዓመት 1.2 ሚሊዮን ቱሪስቶች (ካለፉት 5 ዓመታት የ50 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል) ተስተናግደዋል፡፡ ደም የማፍሰስ ጥማት የነበረበት የኢዲ አሚን አገዛዝ መገርሰሱን ተከትሎ ግን ለበርካታ አስርት ዓመታት የአገሪቱ ቱሪዝም አንዳችም እንቅስቃሴ አልነበረውም፡፡
ዌኬሳ ከመወለዱ ሁለት ዓመታት በፊት ነበር አምባገነኑ ኢዲ አሚን፤ አገሪቱን በሃይል በቁጥጥሩ ስር ያደረጋት፡፡ ራሱን የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንት አድርጐ የሾመው አሚን፤ የብሪቲሽ ኢምፓየር ድል አድራጊና የስኮትላንድ የመጨረሻ ንጉስ እንደሚሆን አውጆ ነበር፡፡ (The Last King of Scotland የሚል ፊልም መሰራቱን ልብ ይሏል) “ቢግ ዳዲ” ተብሎ መጠራትንም ይወድ ነበር፡፡ የአገሬው ሰው ግን የሽብር አገዛዙን የሚመጥን  የተለየ ቅጽል ስም አወጣለት - “የኡጋንዳው ጨፍጫፊ” በማለት፡፡
“እኔ በተወለድኩበት ወቅት ለእያንዳንዱ ኡጋንዳዊ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር፡፡

በኢኮኖሚው ረገድ ብዙ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ሰዎች በህይወት ለመቆየት የማይፈነቅሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡” ሲል ፈታኙን የልጅነት ዘመኑን አስታውሷል፡፡
“ቤተሰቤ ለድንበር አካባቢ ቅርብ ነበር፤ ማድረግ የሚችሉት ብቸኛ ነገር ከኬንያ ሸቀጦችን በኮንትሮባንድ ማስገባት ነበር፡፡ እኔም በ7 ዓመት የልጅነት ዕድሜዬ በህገወጥ መንገድ ሸቀጦችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የተሳተፍኩ ይመስለኛል” ብሏል - ዌኬሳ፡፡
የ50 ሳንቲም ደሞዝ
ከአንዱ ወደ ሌላው እያለ ብዙ ሥራዎችን ተቀጥሮ ሰርቷል፡፡ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በወር 10 ዶላር (200 ብር ገደማ) እየተከፈለው ወለል ያፀዳ ነበር፡፡ “ሃቁን ለመናገር የአንድ ሳምንት በጀቴ ግማሽ ዶላር (50 ሳንቲም) ነበር” ይላል፡፡  ቱሪስቶችን የማስጐብኘት ሥራ ማግኘቱ ግን የማታ የማታ የህይወት አቅጣጫውን ቀየረለት፡፡ እሱም ቢሆን ግን አድካሚ እንደነበር አልደበቀም፡፡
“የመጀመሪያ ጉዞዬን በደንብ አስታውሳለሁ፡፡ ሦስት ቱሪስቶች ይዘን ለ15 ቀን ገደማ ነበር የሄድነው፡፡ ሜዳ ላይ ድንኳኖችን መትከል ነበረብን፤ ለቱሪስቶቹ ቁርስ እናዘጋጃለን፤  ሜዳ ላይ የሚቀጣጠለውን እሳት (ካምፕፋየር) የመጨረሻው ሰው እስኪነሳ ድረስ (እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ሊሆን ይችላል) መቆስቆስ የግድ ነው፤ በጣም አድካሚ ስራ ነበር” በማለት የመጀመሪያ የአስጐብኚነት ሥራውን ያስታውሳል፡፡
እ.ኤ.አ በ2001 ዓ.ም የራሱን ድርጅት ለማቋቋም ሲወስን ማንም ያበረታታው አልነበረም፡፡ እንኳን ማበረታታት እንደ ፍጥርጥሩ እንዲሆን እድል አልተሰጠውም፡፡ የሚያውቁት ሁሉ “ከድሃ ቤተሰብ ስለተወለድክ፤ ቢዝነስ መስራት አትችልም” ይሉት እንደነበር ይናገራል፡፡ እንዲህ የሚሉት ጥቂት ሰዎች ቢሆኑ ይቋቋመው ነበር፡፡ ችግሩ ሁሉም ሰው አንድ አቋም መያዙ ነበር፡፡
“በዙሪያዬ ከከበቡኝ ሰዎች 99 በመቶው ‘የቢዝነስ መሰረት ስለሌለህ አይሳካልህም’ ይሉኝ  ነበር፡፡ እኔ ግን አሁንም ድረስ እግዚአብሔር ይሄን ዕድል የሰጠኝ ሊፈትነኝ እንደሆነ አስባለሁ፤ እናም በዚህ ሥራ ስኬታማ መሆኔን ማረጋገጥ እሻለሁ” ብሏል፡፡እንዲህ ይበል እንጂ ስኬቱን አረጋግጧል፡፡ ዛሬ ዌኬሳ ሚሊዬነር ሆኗል፡፡ ከራሱ ተርፎ በአስጐብኝነት ዕውቅና በተቀዳጀው  ኩባንያው አማካኝነት ለ180 ኡጋንዳውያን የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
“ኩባንያው በአገሪቱ ከሚታወቁት 3 ምርጥ የአስጐብኚ ኩባንያዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ እኔን ከሚያስደስቱኝ ነገሮች አንዱ ግን በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ የመኝታ ክፍሎችን በመገንባት የመጀመሪያው ኡጋንዳዊ መሆኔ ነው፤  ብዙ ኡጋንዳውያንም ተመሳሳይ ግንባታ ለመጀመር እያኮበኮቡ ነው፡፡” ሲል ለሲኤንኤን ገልጿል፡፡
አሁን በርካታ ኡጋንዳውያን “ዌኬሳ መስራት ከቻለ፤ እኛም አያቅተንም” እያሉ እንደሆነ ይናገራል፡፡ “ከድሃ ቤተሰብ ስለተወለድክ ቢዝነስ መስራት አትችልም” የተባለው ዌኬሳ፤ ዛሬ ለአያሌ ኡጋንዳውያን የብርታትና የመነቃቃት ምንጭ ለመሆን ችሏል፡፡ የስኬት ምስጢሩ በተለያዩ ሰዎች አስተያየት ሳይወናበዱ የራስን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በፅናት መትጋት  እንደሆነ ከዚህ የቢዝነስ ጀግና መማር አያዳግትም፡፡ ሠናይ ሰንበት ይሁንላችሁ!!

                  ለፈረንሳይ ቡና ያቀርብ የነበረ አንድ ቡና ላኪ ድርጅት “እናዝናለን፣ ያቀረብከው ቡና የአገሪቱን የጥራት ደረጃ መመዘኛ ስለማያሟላ ልንቀበልህ አንችልም” ተብሎ፣ ቡናውን ይዞ መመለሱን አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ በምታቀርባቸው የተለያዩ የግብርና ምርት ውጤቶችም ላይ ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚከሰቱ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡
ለአንድ ነጋዴ ወይም የቢዝነስ ሰው፣ ለውጭ ገበያ የላከው ምርት “የእኛን አገር የጥራት ደረጃ (ስታንዳርድ) አያሟላም” ተብሎ ውድቅ ሲደረግበት ከሚደርስበት ኪሳራና ውርደት፣ እፍረትና ቅሌት፣ … የበለጠ አደጋ ያለ አይመስለኝም፡፡
ለምርት ግዢ፣ ለዝግጅት፣ ለትራስፖርት፣ ለሰራተኞች ደሞዝ፣ ለመንግስት የሚከፈል ግዴታ፣ … አጠቃላይ ወጪውን ከመክሰሩም በላይ ከንግድ ሸሪኩ ጋር ከተስማማበት የጥራት ደረጃ በታች በማቅረቡ እምነት የሚጣልበት ስላልሆነ ውላቸው ይፈርሳል፡፡ የችግሩ ምክንያት የግብርና ምርት ውጤቱ ወደ ውጭ ከመላኩ በፊት የተቀባዩን አገር ስታንዳርድ ወይም ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ “ያሟላል” ወይም “አያሟላም” የሚል ተቋም ወይም ላቦራቶሪ በአገር ውስጥ ባለመኖሩ ነበር፡፡
አሁን ይህን ችግር የሚቀርፍ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የመመርመሪያ (የፍተሻ) ላቦራቶሪ በአገር ውስጥ ተቋቁሟል፡፡ ብሌስ አግሪ ፉድ ላብራቶሪ ሰርቪስ ኃ.የተ.የግ.ማ ይባላል፡፡ ላቦራቶሪው “በለጠና ቤተሰቡ” የተባለ አገር በቀል ድርጅት 51 በመቶ፣ ኢኒክስ ዴቨሎፕመንት (Onyx Development) በተባለ የፈረንሳይ ኩባንያ 49 በመቶ ድርሻ በመያዝ፣ በ80 ሚሊዮን ብር በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል፡፡ ባለፈው ሳምንት በክብር እንግድነት ተገኝተው ላቦራቶሪውን  የመረቁት በምክትል ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የኮሙኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል ናቸው፡፡ ዶ/ር ደብረጽዮን በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር አገሪቷ፣ ሁለተኛውን ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ብቃት ያላቸውን ላቦራቶሪዎች በከፍተኛ ደረጃ በምትፈልግበት ወቅት፣ “ብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ ሰርቪስ”  በመቋቋሙ፣ የምግብ ደህንነትን፣ ጥራትና የኑትሪሽን ይዞታቸውን በማረጋገጥ ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ የምግብ ንግድ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል ብለዋል፡፡
ብሔራዊ የምግብ ኑትሪሽን ፕሮግራምን፣ የምግብ ዋስትና፣ የኤክስፖርት፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉ የዕድገት ስትራቴጂዎችን እንዲሁም የጥራት መሰረተ ልማትና ከሁሉም በላይ ሁለተኛውን ምዕራፍ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እውን ለማድረግ የብሌስ ላቦራቶሪ ተልዕኮና ራዕይ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ መንግስት፣ ላብራቶሪውን ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም አለው ብለዋል፤ ዶ/ር ደብረጽዮን፡፡
በብሌስ አግሪ ፉድ ላብራቶሪ ሰርቪስ የቴክኒክና የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ሙላት አበጋዝ፤ የብሌስ ላቦራቶሪ ለአገሪቷ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው በዋናነት በአገሪቱ ውስጥ በምግብ ደህንነት ጉድለት የሚመጡ ችግሮችን በላቦራቶሪ በመፈተሸ ለህብረተሰቡና ለአምራቾች፣ ለመስሪያ ቤቶችና ለመንግሥት ማሳወቅ ነው ብለዋል፡፡
ብሌስ፣ ይህን ተግባር እውን ለማድረግ የፍተሻ ላቦራቶሪ ማደራጀቱን የጠቀሱት ዶ/ር ሙላት፣ በተወሰኑ ፍተሻዎች ላይ ማለትም የካንሰር መንስኤ እንደሆነ የሚነገረውን በጥራጥሬ ምርቶች ውስጥ የሚገኘውን አፍላቶክሲን እንዲሁም ለካንሰር በሽታ ምክንያት ይሆናል የተባለውን በቡናው ውስጥ የሚገኝ አክራቶክሲን የተባለ ኬሚካል በመለየትና የማይክሮ ባዮሎጂ ምርመራዎች በማድረግ ከአይኤስኦ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
ማይክሮ ባዮሎጂ ሲባል የምግብ ወለድ በሽታ የሚሆኑትን ባክቴሪያዎች መለየት የሚያስችል አቅም አጎልብቷል ማለት ነው፡፡ የምግብ ደህንነትን በመለየት የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ የመጀመሪያው ሥራችን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በአገራችን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት (ማልኑትሪሽን) አለ፡፡ ላቦራቶሪው ይህን የምግብ እጥረት መፈተሽ የሚያስችል አቅም አለው፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚቀርቡልንን ምግቦች የፕሮቲን፣ የስብ (ፋት)፣ የካርቦሃይድሬትና የኢነርጂ፣ … ይዘት ወይም መጠን መፈተሸ እንችላለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ወደፊት ደግሞ ከአውሮፓ የገዛናቸው መሳሪዎች ተተክለው ስራ ሲጀምሩ ቫይታሚን፣ አሚኖ አሲድ፣ ፋቲ አሲድ፣ ስኳር፣ … በተባሉ ዘርፎች ሰፊ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ይህም ፋብሪካዎች፤ ህብረተሰቡ የተመጣጠነ የምግብ ይዘት እንዲያገኝ የሚያስችል ምግብ እንዲያመርቱ ያግዛቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሶስተኛው የላቦራቶሪው ተግባር የኤክስፖርቱን ዘርፍ ማገዝ ነው ያሉት ዶ/ር ሙላት፤ አገራችን ወደ ውጭ የምትልካቸው በርካታ ምርቶች አሉ፡፡ እዚህ ምርቶች በላቦራቶሪ ደረጃ ተፈትሸው ይዘታቸው ካልታወቀ በስተቀር፣ የውጭ ገበያ አግኝቶ ለመወዳደር አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን ከ30 በላይ ኢንዱስትሪዎች፣ አምራቾችና የተለያዩ የውጭ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ሲልኩ የምግብ ደህንነት ህክምና፣ ጥራትና ቀመሩን በመስጠት ከፍተኛ እገዛና እየሰጠን ነው፡፡
ሌላው ደግሞ የተደራጀ የሥልጠና ማዕከል አዘጋጅተናል፡፡ ወደፊት፣ ለተጠቃሚው፣ ለኢንዱስትሪው፣ ለአምራቾችና ለመንግስት መ/ቤቶች፣ … ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ በተጨማሪም የምርምርና የልማት ማበልፀጊያ ማዕከል አለን፡፡ በዚህ ዘርፍ ከራሳችን በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም ከምርምር ማዕከላት ጋር ለመተባበርና እሴት በሚጨምሩ ነገሮች  ላይ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ዝግጅታችንን አጠናቀናል በማለት ላቦራቶሪው የሚሰራቸውን ዋና ዋና ተግባሮች አስረድተዋል፤ ዶ/ር ሙላት አበጋዝ፡፡
ላቦራቶሪው የተሟላና ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ ነው ስንል፣ በመፈተሻ መሳሪያዎች ብቻ ሳይሆን በባለሙያዎችም ጭምር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የምንወዳደረው ብዙ ልምድና እውቀት ካላቸው ዓለም አቀፍ ላቦራቶሪዎች ጋር ነው፡፡ የእኛን የፍተሻ ውጤት የተጠራጠረ አካል፣ በሌላ ላቦራቶሪ አስመርምሮ ውጤቱ እኛ ከሰጠነው ጋር ተመሳሳይ ካልሆነ አደጋ አለው፡፡ ስለዚህ ባለሙያዎቻችን በሙሉ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ከመሆናቸውም በላይ ልዩ የላቦራቶሪ ፍተሻ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፤ ወደፊትም ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የእውቀት ማሻሻያ የሥራ ላይ ስልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል፤ ዳይሬክተሩ፡፡
ላቦራቶሪው እስካሁን ድረስ ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የግብርናና የምግብ ምርቶችን ናሙና ለመፈተሽ ወደተለያዩ አገሮች በሚደረግ ጉዞ የሚባክነውን ጊዜ ያስቀራል፡፡ ወጪን ይቀንሳል ያሉት የላቦራቶሪው ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሕሊና በለጠ፤ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የግብርናና የምግብ ምርቶችን ደህንነትና ጥራት ለማረጋገጥ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ ሕሊና፣ አስተማማኝና ጥራት ያለው የፍተሻ፣ ምርምርና ስርፀት፣ የስልጠናና የኮንፈረንስ አገልግሎት በመስጠት፣ በግብርና ምርት ዘርፎች በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ አምራች አርሶ አደሩን፣ የምግብ ነክ ፋብሪካ ባለሀብቱን፣ የምግብ ባለሙያዎችን፣ ተመራማሪውን፣ ነጋዴውና ህብረተሰቡን ማስተባበር ዋናው ዓላማቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመልማት ላይ ባሉ አገሮች በተመጣጠነ ጤናማ ምግብ እጥረት በርካታ ሕፃናት በለጋ ዕድሜያቸው ይሞታሉ ያሉት ስራ አስኪያጇ፤ በኢትዮጵያም በዚሁ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት 67 በመቶ ህዝብ ለአቀንጭራ የተጋለጠ ሊሆን፣ አኀዙ በአሁኑ ወቅት በህፃናት ወደ 44 በመቶ ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በአካልና በበሽታ መልኩ 54 በመቶ ህፃናት ለአኒሚያ ወይም በተለምዶ ደም ማነስ እየተባለ ለሚጠራው በሽታ የተጋለጡ እንደሆነ የገለፁት ወ/ሮ ሕሊና፤ በእውቀት፣ በአዕምሮ ብስለትና በምርታማነት ዝቅተኛ እንድንሆን አድርጎናል በማለት አስረድተዋል፡፡
ሀገራችን ይህንን ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ ችግር ለመቅረፍ ሀገር አቀፍ የሥነ-ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም የእርሻና የምግብ ውጤቶች ምርትና ኤክስፖርት ንግድ ሁለተኛውን ዙር የዕድገት ፕላን ያዘጋጀች በመሆኑ ብሌስ ይህንን ራዕይ ለማሳካት፣ በግብርና፣ በምግብ ውጤቶች፣ በውሃና አፈር፣ በምግብ ደህንነትና ጥራት፣ በእንስሳትና ዕፅዋት ጤንነት፣ በምግብ ምርት ቴክኖሎጂ፣ በላቦራቶሪ ፍተሻ፣ በስነ-ምግብ ቀመር… አያያዝና አጠቃቀም… ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል አቅም ማዳበሩን ስገልጽ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል፡፡   

         ባለፈው ሳምንት ቡርኪናፋሶን ለ27 ዓመታት እንደ ግል ንብረታቸው ሲያዙባት የከረሙት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ፤ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ሲሉ ህገመንግስቱን ለማሻሻል ያደረጉት (ንቀትና ድፍረት የተቀላቀለበት ነው) ሙከራ ያስከተለው ውጤት ያልጠበቁት ነበር፡፡ (አመዳቸውን ቡን ሳይል አልቀረም!) ምንም ቢሆን የህዝብ አመፅ አይጠብቁማ፡፡ መቼም የሥልጣን እህል ውሃቸው ቢያልቅ ነው እንጂ አምባገነኖች እንዲህ በቀላሉ ከቤተመንግስት እኮ አይወጡም፡፡ (ያውም በአንዲት ቀን አብዮት?!) አመጽና ተቃውሞን በሃይል ለመመከትና ለማፈን ሁሌም ታማኝና አስተማማኝ ወታደራዊ ኃይል ከጎናቸው አይጠፋም፡፡ የስልጣን ገመዳቸው ተበጠስ ያለው ጊዜ ግን ወታደሩም ፊቱን ያዞርባቸዋል፡፡ በአምባገነኖቹ የአፍሪካ መሪዎች በእነ ጋዳፊ፣ ሁስኒ ሙባረክ…አይተነዋል፡፡
የአምባገነን መሪዎችን ባህሪና ነገረ ስራ እንደ አዲስ ለመፈተሽ ያነሳሱኝ (Inspiration ሆነውኛል!) ከስልጣን ከተወገዱ የሳምንት ዕድሜ ብቻ ያስቆጠሩት የቡርኪናፋሶው የቀድሞ መሪ ናቸውና ምስጋና ይገባቸዋል (አምባገነን ማመስገን ነውር ነው እንዳትሉኝ!) እናላችሁ ፍተሻዬን ውጤታማ ለማድረግ በአምባገነን መሪዎች ዙሪያ ያልበረበርኩት መረጃ የለም፡፡ (ዕድሜ ለእነ ጐጉል!) የእያንዳንዱን አምባገነን ታሪክ (ሥልጣን ከተቆናጠጠበት እስከተገረሰሰበት) በሰከንዶች ቅጽበት ማግኘት ይቻላል፡፡ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ባልተከበሩበት አገር፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሊስፋፋ እንደማይችል ልብ ይሏል፡፡ (ነፃነት ሳይኖር ፈጠራ እሺ አይልም!) በነገራችሁ ላይ “ስኬታማ አምባገነን የመሆን ምስጢር” በሚል ርዕስ በታተመ መጽሐፍ ላይ እንዳነበብኩት፤ አምባገነን መሪዎች በአገር ስም ብዙ ገንዘብ እየተበደሩ፣ ቀጣዩን ትውልድ ለዕዳ በመዳረግ ዝነኛ ሲሆኑ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ደሞ ዳተኞች ናቸው፡፡ አቅም በማጣት ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ አንዳንዴ ሆን ብለው ነው፡፡ መንገድ ከተስፋፋ የሚቀናቀናቸው የፖለቲካ ቡድን ከሸመቀበት ወጥቶ ቤተመንግስት ድረስ ዘው እንዳይል ክፉኛ ይሰጋሉ፡፡ (የስልጣን አወጣጣቸውን ያውቁታላ!!)
እናላችሁ… ዛሬ የጥቂት አምባገነን መሪዎችን እንግዳ ባህርያት አብረን እየቃኘን እንደመም፡፡ እናንተ…ሥልጣን እንዲህ ያሳብዳል? ሥልጣን እንዲህ ያቃዣል? ሥልጣን እንዲህ ያስዋሻል? ሥልጣን እንዲህ ያስቀላምዳል? በሉ አብረን “አጃኢብ” እንበል፡፡
ራሳቸውን “የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንት” ብለው በመሰየም የሚታወቁት የሃይቲው የቀድሞ አምባገን መሪ (እ.ኤ.አ ከ1907-1971 ገዝተዋል) ፍራንሶይስ ዱቫሊየር፤ ለ14 ዓመት የዘለቀው የስልጣን ዘመናቸው በጥርጣሬና በፍርሃት የተሞላ ነበር፡፡ (ሥራቸው እኮ ነው የሚያስፈራቸው!?) በነገራችሁ ላይ በየትኛውም የዓለም ክፍል የነበሩና ያሉ አምባገነኖች በአብዛኛው ይመሳሰላሉ (ለእነሱ “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር” አይሰራም!) እናላችሁ… የሃይቲው አምባገነንም ቢፈሩና ቢጠራጠሩ አይፈረድባቸውም፡፡ አንደኛ የፈፀሙትን ግፍና ጭካኔ ያውቁታል፡፡ ሁለተኛ ሥልጣን አንዴ ከእጅ ከወጣ አይመለስም፡፡
ዱቫሊየር ለስልጣናቸው ስጋት የመሰሏቸውን ሁሉ አንድ በአንድ አስወግደዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን (ቦይ ስካውቶችን ሳይቀር) ያገዱ ጠርጣራ መሪ ነበሩ፡፡ ባዕድ አምልኮ የተጠናወታቸው የሃይቲው የቀድሞ መሪ፤ ወር በገባ በ22ኛው ቀን የሚጠብቀኝ መንፈሳዊ ኃይል አለ ብለው ያምኑ እንደነበር ይነገራል፡፡ በስልጣን ዘመናቸው የመጨረሻ ዓመታትም ወር በገባ በ22ኛው ቀን ብቻ ነበር ከቤተመንግስት የሚወጡት፡፡ (ስልጣን ሊያልቅ ሲል ያሳሳል!)  
አንዴ የሃይቲ የፓርላማ ቡድን መሪ የነበሩ ክሊመንት ባርቦት የተባሉ የፖለቲካ ተቀናቃኛቸው፤ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገውባቸው ተሰውረው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ እኚህ “ህገመንግስት በሃይል ለመናድ” የሞከሩ ተቀናቃኝ፤ ከተሸሸጉበት ተይዘው እንዲመጡላቸው ለፖሊስ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ ሆኖም ፖሊስ “አስሼ አስሼ አጣኋቸው” ይላቸዋል፡፡ ይሄኔ ዱቫሊየ ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “ባርቦት ራሱን ወደ ጥቁር ውሻ ቀይሮ ነው” አሉና አረፉት፡፡ ከዚያም በሃይቲ የሚገኙ ጥቁር ውሻዎች በሙሉ እንዲገደሉ አዘዙ (የሃይቲ ውሾች ሳይቀሩ የአምባገነን ሰለባ ሆኑ!) የማታ ማታ ግን የተሰወሩት ባርቦት ተገኙ፡፡ እሳቸውንም አልማሯቸውም፡፡ የሞት ቅጣት ፈረዱባቸው፡፡ ጭንቅላታቸውን ቆርጠውም ለሚያምኑበት ባዕድ መንፈስ እንዳስቀመጡለት ይነገራል፡፡
አንድ ጊዜ ምን እንደታያቸው አይታወቅም፡፡ ምርጫ ይካሄድ አሉ - ነፃ ምርጫ፡፡ 100 ፐርሰንት ድምፅ አግኝተው አሸነፉ (ድንቄም ነፃ ምርጫ!) በነገራችሁ ላይ እኚህ አምባገነን መሪ ስድስት የግድያ ሙከራዎችን (በራሳቸው ጥበብ ይሁን በባዕድ መንፈስ ኃይል አልታወቀም!) ...አምልጠዋል፡፡ በመጨረሻም የተወሰነ ጊዜ ታመው እ.ኤ.አ በ1971 ዓ.ም ሞቱ፡፡ ህዝቡ እሳቸውን ቢገላገልም የሥልጣን መንበሩን የተረከበው ልጃቸው ነበር፡፡
ወደ አፍሪካ ስንመጣ የቀድሞውን የኡጋንዳ አምባገነን መሪ ኢዲ አሚንን (ከ1920-2003) እናገኛለን፡፡ እኚህን አምባገን ሳስባቸው የስፔናዊው ደራሲ ሴርቫንቴ “ዶን ኪሆቴ” መፅሃፍ ላይ ያለው ዋና ዶን ኪኾቴ የተባለ ገፀ ባህርይ ትዝ ይለኛል (አወይ መመሳሰል አሉ!) ራሳቸውን “የህይወት ዘመን ፕሬዚዳንት”፣ “የታላቋ ብሪታኒያ ግዛት አስገባሪ”፣ “የስኮትላንድ የመጨረሻው ንጉስ” እያሉ የሚጠሩት ኢዲ አሚን፤ ፊልድ ማርሻል የተባለውን የመጨረሻ ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ ለራሳቸው የሸለሙ ዕብሪተኛ መሪ ነበሩ፡፡
የኢዲ አሚን አስገራሚና ቅጥ አምባሩ የጠፋ ባህርይ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ የአንድ ታዋቂና ሃብታም እስያዊ ቤተሰብ ልጅ የሆነች ኮረዳን ለትዳር ጠይቀው አዎንታዊ ምላሽ ያላገኙት አሚን፤ የአፀፋ እርምጃቸው አስደንጋጭ ነበር፡፡ በኡጋንዳ የሚኖሩ እስያዊያንን በሙሉ ከአገሪቱ አባረሩ፡፡ (እብሪት ነው እብደት?) የአፍሪካ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የሰሩት አስገራሚ ድራማም ተጠቃሽ ነው፡፡ ወደ ስብሰባው አዳራሽ የገቡት ዙፋን በሚመስል ወንበር ላይ ተቀምጠውና አራት ነጮች ከእነ ወንበራቸው ተሸክመዋቸው ነበር፡፡ የዚህን ምክንያት በአግራሞት ለተሞሉት የአፍሪካ ሚኒስትሮች ሲያስረዱም፤ “እኛ አፍሪካውያን አውሮፓውያንን ስንሸከም ኖረናል፡፡ አሁን ደግሞ የሚሸከሙን እነሱ ናቸው፡፡ እኛ አሁን ጌታ መሆናችንን ለማሳየት ብዬ ነው” አሉ - ሞኝ ይሁኑ ብልህ የማይታወቁት አሚን፡፡ ኢዲ አሚን ይሄ ተግባራቸው እንዳሰቡት አድናቆትን አላተረፈላቸውም፡፡ እንደውም በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ክፉኛ አስተችቷቸዋል (ሌሎቹም ከእሳቸው ብዙ ባይለዩም!)
ኢዲ አሚን፤ ዋና ፉክክራቸው ከእንግሊዟ ንግስት ኤልዛቤት ጋር ነበር (ንግስቲቷ ነገሬ ባትላቸውም!) እናም አንድ ጊዜ “የጋራ ገበያ አገራት ሊቀመንበር መሆን ያለብኝ እኔ እንጂ ንግስቲቷ አይደለችም” ሲሉ በድፍረት ተናግረው ነበር (አምባገነንነት ላይ እብደት ሲታከልበት ውጤቱን አስቡት!) እኔ መቼም ሰውየው “አምባገነን ነበሩ” በሚል ብቻ አላልፋቸውም፡፡ እንዴ ከዚህ የበለጠ እበደት አለ እንዴ? በነገራችሁ ላይ አሚን…ለንግስት ኤልዛቤት በርካታ የፍቅር ደብዳቤዎችን እንደፃፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ (ንግስቲቱ ምን ብለው ይሆን?)
አምባገነኑ መሪ፤  ዋና ዋና የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን አድራሻ በማጥፋት የሚደርስባቸው አልነበረም፡፡ እንዴት? ለኢዲ አሚን ቀላል ነበር፡፡ ያስገድሏቸዋል፡፡ ይገድሏቸዋል፡፡ የእሳቸው ነገር በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የሰው ስጋ ይበሉ ነበር ይባላል፡፡ ተቀናቃኞቻቸውን ካስገደሉ ወይም ከገደሉ በኋላ  አንድም ራሳቸው ይበሏቸዋል አሊያም ደሞ ለለማዳ አዞዎቻቸው ቀለብ ያደርጓቸዋል ይባል ነበር፡፡ ይሄ በሁነኛ ማስረጃ ባይረጋገጥም በአንድ ወቅት አማካሪያቸውን ከእራት በፊት ጠርተው፤ “ያንተን ልብ እፈልገዋለሁ፤ ልጆችህንም ልበላቸው እሻለሁ” በማለት ክው እንዳደረጉት ተዘግቧል፡፡
አሚን ከአምስት በላይ ሚስቶች የነበራቸው ሲሆን (በተመሳሳይ ጊዜ እኮ ነው!) ከእነዚህ ሚስቶቻቸውም ከደርዘን በላይ ልጆችን ወልደዋል፡፡ አሳዛኙ ነገር አንደኛዋ ሚስታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ ፍሪጅ ውስጥ መገኘቷ ነው፡፡ (የአምባገነንነት መጨረሻ ጭራቅነት ሳይሆን አይቀርም!!)
እ.ኤ.አ ከ1940-2006 ዓ.ም የቱርክሜኒስታን ፕሬዚዳንት የነበሩት ሳፓርሙራት ኒያዞቭ ደግሞ በህዝባቸው ውስጥ የራሳቸውን አምልኮተ-ስብዕና በመገንባት ወደርየለሽ ነበሩ፡፡ 15 ሜ. (50 ጫማ) ቁመት ያለው የወርቅ-ቅብ ሃውልታቸውን በቁማቸው ያሰሩ ዕብሪተኛ መሪ ናቸው፡፡ ሃውልታቸው ሁልጊዜ ፊቱ  ወደ ፀሐይ አቅጣጫ እንዲሆን ታስቦ የሚሽከረከር ሆኖ ነበር የተሰራው፡፡
ፎቶአቸውን በየግንቡና በየህንፃው ላይ ማየት የሚያስገርም አልነበረም፡፡ በአገሪቱ የገንዘብ ኖቶች ላይ ሳይቀር ምስላቸው ነበረ፡፡ አብዛኛው ህዝብ በድህነት ሲዳክር በነበረበት በዚያ ዘመን ኒያዞቭ፤ በበረሃነቷ በምትታወቀው ቱርክሜኒስታን እምብርት ላይ ግዙፍ የበረዶ ቤተመንግስት ያሳነፁ አምባገነን ነበሩ፡፡ (በነገራችሁ ላይ ሰሞኑን ቢቢሲ እንደዘገበው፤ የአሁኑ የቱርክ መሪ ከ600 ሚ.ዶላር በላይ አውጥተው ያሳነፁት ቤተመንግስት የህዝብ ተቃውሞ አስነስቷል!) አምባገነኖች አንድ ናቸው አልተባባልንም!
ሰውየው እልም ባለ በረሃ ላይ ሰው ሰራሽ ሃይቅ እንዲገነባላቸውም ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፤ ይሰራ አይሰራ ባይገለፅም፡፡ እኚህ አምባገነን እንደ ሌሎች አምባገነኖች ሁሉ ሥልጣን በያዙ ማግስት የመጀመሪያ ሥራቸው ያደረጉት የመንገዶችን፣ ህንፃዎችን፣ ከተሞችን፣ ፓርኮችን ወዘተ… ስያሜዎች መቀየር ነበር (አብዛኞቹን በራሳቸው ስም ሰይመዋቸዋል!) ይሄ ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡ (አምባገነን ሁሉ ያደርገዋላ!) በጣም  የሚገርመው ግን ምን መሰላችሁ? የዓመቱን ወራት… እነ ጃንዋሪ፣ ፌብሯሪን በራሳቸው፤ በቤተሰባቸውና በመጽሐፋቸው ስም መሰየማቸው ነው፡፡ (አጃኢብ እኮ ነው!) ሌላው ቀርቶ Bread ወይም “ዳቦ”ን እንኳን አልተውም፡፡ በእናታቸው ስም ሰይመውታል፡፡
አምባገነኑ የቱርክሜኒስታን የቀድሞ መሪ ይበልጥ የሚታወቁት ግን በደነገጓቸው አስገራሚ ህጐች ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም ሲጋራ ማጨስ ማቆማቸውን ተከትሎ ሚኒስትሮቻቸው በሙሉ እንደሳቸው ማጨስ እንዲያቆሙ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡ እንደ ሳዳም ሁሴንና ጋዳፊ ሁሉ እሳቸውም መፅሃፍ ፅፈዋል፡፡ (አምልኮተ - ስብዕና የመገንባት አባዜ እኮ ነው!)የመፅሃፉ ርዕስ “ሩክህናማ” ወይም “የነፍስ መፅሃፍ” የተሰኘ ሲሆን ትክክለኛውን መንገድ የሚያስተምርና ከአሉታዊ ተፅዕኖዎች የሚከላከል እንደሆነ ይነገርለት ነበር፡፡ የሚያስገርመው ታዲያ ምን መሰላችሁ? ይሄ መፅሃፍ በት/ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት መደረጉ ነው፡፡ በዚህ ብቻ ግን አያበቃም፡፡ የመንግስት ሠራተኞች ከስራቸው እንዳይባረሩ ከፈለጉ መጽሐፉን በቃላቸው መሸምደድ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ዜጐች የመንጃ ፈቃድ ሊያወጡ ሲሉ ዋናው መስፈርት የፕሬዚዳንቱን መጽሐፍ ከጫፍ እስከጫፍ እጥብ ማድረግ ነው፡፡ ከመጽሐፉ የወጡ ጥያቄዎችን በተገቢ ሁኔታ ያልመለሰ መንጃ ፈቃድ አይሰጠውም፡፡ (የአምባገነንነትን ጥግ አያችሁልኝ!) ፕሬዚዳንቱ የደነገጓቸውን ህጐች ረሳናቸው እኮ፡፡ ወንዶች ፀጉርና ፂም እንዳያስረዝሙ እገዳ ተጥሎባቸው ነበር፡፡ ለቲቪ ዜና አቅራቢዎች ሜክአፕና የወርቅ ጥርስ አይፈቀድም ይላል - ህጋቸው፡፡
አምባገነኑ የቱርክሜኒስታን የቀድሞ ፕሬዚዳንት የፈረስ አፍቃሪ ነበሩ፡፡ ይሄን ፍቅራቸውን ለመወጣትም በ20 ሚ.ዶላር የፈረስ መዝናኛ ማዕከል ያስገነቡ ሲሆን ማዕከሉ የመዋኛ ገንዳ፣ የአየር ማቀዝቀዣና የህክምና አገልግሎቶች የተሟሉለት ነበር፡፡ (ይሄ ሁሉ ድሆች በሞሉባት አገር እንደነበር አትዘንጉብኝ!) እኚህ አምባገነን መሪ ከስልጣን የወረዱት በ2006 ዓ.ም ሲሞቱ ነው፡፡ የወርቅ ቅብ ሃውልታቸው ደሞ ከአራት ዓመት በኋላ በ2010 ዓ.ም ከተተከለበት ስፍራ ተወግዷል (ደርግ ሲገረሰስ የተገነደሰው የሌኒን ሃውልት ትዝ አለኝ!) እሳቸውን የተኳቸው ፕሬዚዳንት ደግሞ የፈረስ የቁንጅና ውድድር በ2011 እንዳዘጋጁ ተዘግቧል  (ማለቂያ የሌለው የአምባገነኖች እብደት…አትሉም!)
እኔ ሳስበው ግን አምባገንነት የአገዛዝ ሥርዓት ወይም የግለሰቦች ባህርይ (ስብዕና) አይመስለኝም፡፡ እብደት ወይም ለእብደት አንድ ሃሙስ የቀረው የአዕምሮ መታወክ በሽታ ነው፡፡ ፍርሃት…ጥርጣሬ…ቅዠት…ጀብደኝነት…ጭካኔ…እብሪት…የበሽታው ምልክቶች ናቸው፡፡ የአምባገነንነትን ደዌ እንደ ፖሊዮ ከምድረገጽ ለማጥፋት ብዙ ትጋትና ጥረት ይጠይቃል፡፡ (ከአምባገነንነት የፀዳች ዓለም እኮ ገነት ናት!)

      “አሜሪካ የሚኖሩ የዘሙቴ ማህበር አባላት ‘በዘንድሮው ጉዞ’ ቀንተናል ይላሉ” ብሎ ወዳጄ አጫወተኝ… ዳኜ፣ ድርሻዬ (የካርታው መሀንዲስ)፣ እንዳለ (ቂሾ) ይባላሉ፡፡ የዓመት ሰው ብሏቸው ቢመጡ ደስታዬ ነው፡፡
ዘሙቴ ውስጥ፤ ገና ካፋፍ ላይ ሆነን፣ የአቶ አበበ ወ/ማርያም ቤት ከሩቅ የተንጣለለ ግቢውን በስፋት ዘርግቶ ይታየናል፡፡ ትልቁ ልጃቸውን ግርማን ስለዘሙቴ ቤታቸው ነገረ-ሥራ ጠየኩት፡፡
”ግርማ አበበ ወ/ማርያም ደንቢሶ እባላለሁ” ብሎ ጀመረ፡፡ “ለቤተሰቤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ በ1952 ነው የተወለድኩት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ነው የተወለድኩት፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ቀበሌ 26፡፡ ይችን ሀገር የማውቃት የአባቴ አጎት ሞተው ለለቅሶ መጥቼ ነው - በ1980ዎች፤ 20 ዓመት አካባቢ፡፡ ከዚያ በኋላ መጥቼ አባቴ ይህን ቤት በ1964 ዓ.ም ሣር የነበረውን ቆርቆሮ ቤት አርጎ ሠራ፡፡ እሱ የተወለደው እዚህ ነው፡፡
“አባቴ እዚህ ነው ከናቴ ጋር ከሚስቴ ጋር እዚህ እኖራለሁ” ብሎ መኖር የጀመረው፡፡ እዛው አዲስ ከተማ ሆኖ መርካቶ ሱቅ ነበረው፡፡ ክፍለ ሀገርም ይነግድ ነበር፡፡ እዚህ እንደማንኛውም ሰው ነበር የሚኖረው፡፡ እንሰት ይፍቅ ነበር፤ ጎበዝ ገበሬ ነበር ይባላል፡፡
ከዚያም ቤቱን እየተመላለሰ ያይ ነበር፡፡ “ምን ይሻላል ቤት እንስራ?”  ስንለው “የለም እኔ ሰርቻለሁ” አለን - እዚህ ያንን ቤት ሰርቶ ስለነበር፡፡ በጣም ጎበዝና ታታሪ ገበሬ ነበር አባታችን! ዘመዶቹን ይወድ ነበር፡፡ ያለውን ሁሉ ለዘመዶቹ ይሰጥ ነበር፡፡ የሚያገቡም ሰዎች ካሉ ልብስ ገዝቶ፣ ከብት ገዝቶ ይሰጣል፡፡ እዚህም ሲመጡ ተቀብሎ፤ ሥራ ለሚፈልጉ ስራ ሰጥቶ፣ መማር ለሚፈልጉ ት/ቤት አስገብቶ ያስተምር ነበር፡፡ ደርግ መጣና መሬትና ቤት ወሰደበት፡፡ ታመመ፡፡ ቤት መዋል ጀመረ፡፡ በጣም ይበሳጭ ነበር፡፡ የሚያከራየውም ቤት ነበረው፡፡ ሱቁንም ወሰዱበት፡፡ ከዛ ተበሳጨ፡፡ ታመመ በቃ፡፡ ቤት ዋለ፡፡ እኛም አይዞህ እያልን ትምህርታችንን እያቋረጥን ወደ ሥራ ገባን! 4 ወንዶችና 2 ሴቶች ነን፡፡ አንዷ ሴት በህመም ሞተች፡፡ አባቴ በ1920 ተወልዶ በ1995 ዓ.ም ሞተ፡፡ እናታችንም በ99 ዓ.ም ሞተች፡፡ እሷ እንኳ እነኚህን ቤቶች ሁሉ አይታለች የተሰሩትን፡፡ እኔንም የዳረችኝ እዚሁ ቤት ነው፡፡
“አባቴን ምን እናርግልህ? አልነው”
“አግቡ! በተለይ አንተ አግባ!” አለኝ፡፡
“እሺ ብዬ፤ እሱ እንደፈለገው በባህላዊ መንገድ እዚሁ ዘሙቴ ላገባ ወሰንኩ፡፡
እሺ ብዬው፤ ልጅ እንግዲህ ያባቱን ቃል በመሙላት ላይ ታች ይላል አደለ?... በማህል ታመመ፡፡
የኔንም ሰርግ ሳያይ እሱ አረፈ! በ95፡፡ እኔ በ97 አገባሁ፡፡ እዚህ ቤት፡፡
ይሄንን ቤት ያሰራነው እኔ፣ ኪዳኔ … እናታችንም ነበረች፡፡ እናታችን ቆማ ነው ያሰራችው፡፡ ሀሳብ እያቀረበች እንዲህ ይሁን እያለች … ፊቱ ወዲህ ይሁን እያለች፡፡ ጓዳ ይኑረው እያለች ነው ያሰራችው፡፡ በራሷ ፕላን! በጣም ጭምት ነች፡፡ ያዲሳባ ልጅ ነች፡፡ ወላጆቿ ደብረ ዘይት ሆነው ከአዲስ አበባ ደብረ ዘይት ሄዶ አምጥቶ ነው አዲሳባ ያገባት፡፡ በ1933 ጣሊያን ሲወጣ ነው የተወለደችው፡፡ ከሱ ጋር የተጋባችው በ1950 ነው፡፡ እኔን በ1952 ወለደች፡፡ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ! ቀጥሎ አስቴር አበበ፣ የሷ ታናሽ ያረፈችው ናት፡፡ ከዛ ኪዳኔ ነው፡፡ ከዛ ወርቁ ይሄይስ መጨረሻ ዮዲት ናት! እንግሊዝ ናቸው ሁለቱ፡፡ ትዳር አላቸው ልጅ ወልደዋል፡፡
እናታችን እኛን ለማሳደግ ያላረገችው ነገር የለም፡፡ ትነግድ ነበር ከተማ መርካቶ፡፡ አንድ ወቅት አባታችን ታሞ እሷ ነበረች የምታኖረን፡፡ ሥራ እንድንለምድ አረገች፡፡ በኋላ እሷን ንግዱን እንድትተው አደረግናት፡፡ አባታችንን አንቱ ነው የምትለው፡፡ አባታችሁ እንዲህ ይሉ ነበር “እንዲህ አረጉኝ! እኔ ለማንም ክፉ አላረኩም! “ክፉ እንደሰራ ሰው ቤቱ ጠፋ” እያለ ይጨነቅ ነበር! ግዴሎትም ይሰራል ብላ፤ ቃሉ ተጠብቆ እንዲሰራ ያረገች እሷ ነች! በ99 ዓ.ም እኛ አገር ቤት ገብተን፣ ለመስቀል፣ እሷን እዛ ቻዎ ብለናት ሁሉን ነገር ሸክፋ አዘጋጅታልን፤ ሁሉን ይዘን ገብተን፤ በድንገት ሞተች ተብሎ ሰው ተላከብን፡፡ ተነስተን ሄድን መስከረም 14 ደብረሊባኖስ ተቀበረች፡፡ በ1999 ዓ.ም፡፡
በዓመት ሶስቴ ያህል ወደ ዘሙቴ እንመጣለን፡፡ ባለቤቴ 4ቴም 5ቴም ትመጣለች፡፡ ለመቆጣጠር፡፡ አንዳንዴ ሁላችን ተሰብስበን እንመጣለን፡፡ ለምሳሌ  በ2006 ወደ 4 ጊዜ መጥተናል፡፡ ማህበሩም ይመጣል፡፡ ማሪያምን እያስቀደሰ ይሄዳል፡፡በሰርጌ ሰሞን በ97 15 ቀን ቆየን! በ1997 ሰዉ ሲተራመስ እኔ እዚህ ነበርኩ፡፡ ሰርጌ ሚያዚያ 30 ነበር ይገርምሃል! ከአንድ ሳምንት በፊት ቀድመን ገብተናል እዚህ፡፡ 15 ቀን ቆይተን ነው ወደ ከተማ የሄድነው፡፡ ምንም የአዲሳባን ግርግር አላየንም፡፡”
የግርማና የባለቤቱ ፎቶግራፍ ግድግዳው ላይ ይታያል፡፡ እሱን እያሳየኝ “የመጀመሪያው ዕለት በባህላዊ መንገድ፣ በሁለተኛው ቀን ደግሞ በዘመናዊ፣ በዚህ አይነት አለባበስ ተጋባን፡፡ ሰኞ እለት፡፡ ባህላዊ ማለት ነጭ በነጭ ተደርጎ እጀ ጠባብ ተለብሶ፤ በፈረስ ሆነን፡፡ የእሷ አባቷ ቤት እዛ ነው፡፡ ከእኛ ጋር ዳገት አትወርድም፡፡ ገብሬል ነው ቤቷ፡፡ ባለቤቴ ዘሙቴ ናት! እዛ ነው ያገኘሁዋት፡፡ እኔ ምንድን ነው አስብ የነበረው ከተማ በፍቅር-ጓደኝነት ኖሬ ትዳር መመስረት ነበር- እንደከተሜ! አባቴ ካለኝ በኋላ ግን የትዳርን ምርጫ ለእግዚአብሔር ነው የሰጠሁት! እንደባህላችን ሽማግሌ ጠራሁ፡፡ ትዳር እፈልጋለሁ…  ሀብታም አልልም፣ ደሀ አልልም ቆንጆ ፉንጋ አልልም የጥሩ ቤተሰብ ልጅ ብቻ ፈልጉልኝ አልኳቸው… ተገኝቷል ተባለ - ልይም አላልኩም! በእውነት እግዚአብሔር ነው የሰጠኝ - መቼ እንዳየሁዋት ታውቃለህ? ሰኞ ማታ!” “ዕውነትክን ነው?” አልኩት ተገርሜ፡፡ “እግዚአብሔርን! እኔ እንግዲህ የከተማ ልጅ ነኝ! ነገር ግን አባቴ አከረረውና አግባ ስላለኝ በቃ! እሱ የታየው ነገር አለ ማለት ነው! እና ይሄንን ነገር እግዚአብሔርን ነው የለመንኩት፡፡ ያልኩትም አልቀረ በጣም ታዛዥ ቆንጆ ልጅ ሰጠኝ፡፡ ትዳሬ ቆንጆ ነው፡፡ እንደውም እቤቴ ስገባ እናቴ ያለች ያለች ነው የሚመስለኝ! (በዚህ ዘመን አይታሰብም) እኔ ሚስት አልመረጥኩም! አሁን ሁለት ልጆች አሉኝ - የ8 እና የ 7 ዓመት፡፡
ያሬድ ሚዜዬ ነው፡፡  መረቀልኝ ሚዜዬ ነው! ወንድሙም ሚዜዬ ነው፡፡ (እነዚህ የማህበሩ አባላት ናቸው እንግዲህ)
97ን ሸውዳችሁ እዚህ አሸሸ ገዳሜ አላችሁ አይደል ስለው ያሬድን፡-
“ቶራ ቦራ እኮ ነው ይሄ!” አለኝ፡፡ ተሳሳቅን!
ቅድመ-አያታችን ደምቢሶ ናቸው ቦታውን የያዙት፡፡ የአባታቸው አገር ዋጮ አካባቢ ነበር፡፡ የቄስ ግብዝና ግማሽ ጋሻ መሬት ተሰጥቷቸው እዚሁ እያገለገሉ ትዳር ያዙ፡፡ ልጆች ወለዱ፡፡ ለያንዳንዳቸው ከፋፍለው ሰጡ፡፡ ይሄ ያያታችን ድርሻ ነው - አያታችን ላባታችን ሰጡ፡፡ እነገድር ገበሬ ማህበር ስር ነው ዘሙቴ ያለው! ወረዳው ቡኢ ነው፡፡ ችግር ካለ ከገበሬ ማህበሩ፣ ከፍ ካለ ቡኢ እንሄዳለን፡፡ ሶዶ ነው ህዝቡ!
እንግዲህ ያን ግቢ ያለምክንያት አልጠቀስኩትም፡፡ የተቀደሰ ግቢ ነው፡፡ የዘሙቴ ማርያምን በዓል ልናከብር የመጣነውና ያረፍነው የአቶ አበበ ወልደማርያም የተንጣለለ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ ቀይ ቆርቆሮው የታየን ገና ከላይ ከጋራው ስንንደረደር ነው፡፡ ዐርበ -ሰፊ ተደርጎ በዘመናዊ ሞድ የተሰራ ሰፊ ቤትና በጉራጌ ባህላዊ አሰራር የተሰራው ሌላው ማረፊያችን ጎን ለጎን ናቸው፡፡ የፍራሽ መአት ዙሪያውን ተሰድሯል፡፡ መልበሻ ክፍል መሳይ ጓዳም አለ፡፡ እዚያ ሻንጣችንን አከማቸን - ልብሳችንን ቀየርን፡፡ ማሪያም ዕሮብ ነው የምትውለው፤ ዛሬ ማክሰኞ ነው፡፡ መስከረም 20፡፡ አረፍ አልን፡፡ ቡና ተፈላ! እንግዲህ ድግሱ ጀመረ!
ያ “ይጠጣል እንጂ አይበላም” የተባለው ክትፎ በአይኔ ላይ ይዞር ጀመር፡፡ ጣባ ጣባችንን ያዝን፡- ዐይቤው፣ ጎመኔው፣ ሌላው ቅጥፍ-ጎመን በአውሮፕላን እንደተሰራ የከተማ ካርታ በድንበር በድንበር ተለይቶ፣ ግን ኩታ ገጠም ሆኖ፤ በገዛ ጣባው ከች አለ፡፡
ክትፎው በራሱ ጊዜ ቆይቶ መጣ፡፡ አፕሬቲቭ ይመስል ዐይቤና ቆጮ መጀመሪያ መጥቷል!
ከዚያ ማወራረጃ የእህል አረቄ ቀጠለ፡፡ ሌላ ዘመናዊ ከባድ ከባድ ማወራረጃም ተንቆረቆረ/ፈሰሰ፡፡ ያለፈው የመስቀሉ መንፈስ እዚህ ዘሙቴ ገና እየተሟሟቀ ነው!   
እነሆ፤ ማስቀደስ፣ ክትፎ መጠጣትና መዝናናት የራሱ መንፈስ አለው! የበዓል ውሎ ሥርዓት መርሆው ይሄ ነው!!
የዘሙቴ ማርያም ዓመታዊ ክብረበዓል ደስ ይላል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ቀሳውስት እየቀደሱ ነው፡፡ ታቦት ሊወጣ ጥቂት ሰዓት ቀርቶታል፡፡ ዙሪያውን በአረንጓዴ ተራራ ተከባ በዛፎች ታጅባ የምትገኘው ጎጆ ቅርፅ ያለባት ባለቆርቆሮ ማርያም ቤተክርስቲያን ልትነግሥ እያኮበኮበች ናት፡፡ ሰው ከርቀት አቅጣጫ በመምጣት ላይ ነው፡፡ እኛ በእንሰት ማህል በቀጫጭን መንገዶች ነው ቁልቁል የመጣነው፡፡ ዓይን የሚያለመልመውን ዛፍ እያየን ለምልመናል፡፡ ይህን ግጥም የፃፈኝ ይሄ የዐይን ትፍሥህት ነው፡፡
“ልብ ሁሉ ለምለም ነው፣ ጉራጌው ፍቅር
ከቅዳሴው ጋራ መንፈሱ ጭምር
ዕምነቱ ኬላ ነው፣ ማተቡ ድንበር፤
ከመሬቱ ደሞ አረንጓዴ ጤፍ
ደሞ ከዚያ በላይ አረንጓዴ ጋራ
ሰማያዊ ሰማይ ከጋራው በላይ
አምላክ አትግደለኝ ዘሙቴን ሳላይ” የሚያሰኝ ነው በሙሉ ቀን መለሰ ቅኝት፡፡ ገበሬዎች ሞባይል ሲሞክሩ አያለሁ፡፡ ሥልጣኔያቸው ደስ አለኝ፡፡ በተክሲያኑ ግቢ ውስጥ አራት አምስት ቤቶች አሉ፡፡ አንድ ረዘም ያለ ቤት ሰምበቴ ቤት ይመስላል ምግብ ያበሳስላሉ - ምናልባት ለበኋላ ጠበል     ፀዲቅ ይሆናል፡፡ ሰፊ ክብ ግቢ ነው፡፡ አስቀዳሹ ምዕመን ቀድሞ ገብቷል፡፡ ውጪ ትንሽ ሰው ነው ያለው፡፡ የጄነሬተር ድምፅ አለ፡፡  በክር አውታር የተንጠለጠሉ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የጌጥ አርማዎች በሦስት አውታሮች ይታያሉ፡፡
ዘማሪያን ወጡ፡፡ ሰው ከየት መጣ ሳይባል ግቢውን ሞላው፡፡ ነጫጭ ልብስና ልብሰ ተክህኖ ፈካ፡፡ ዣንጥላው፣ ከበሮው፣ ባንዴ  እርግብግብታ ፈጠረ፡፡
“እኔስ ማርያምን እወዳታለሁ
እመቤቴ እላታለሁ!”
ዘሙቴ ማርያም አቤት ማማሯ
የዘሙቴ ሆነናል… አሁን አምረናል …” ታቦቱ ወጣ፡፡ ታቦቱ የቤተ ክርስቲያኑን አጥር ሊዞር ነው፡፡ ይኸው ታቦቱን እየተከተልኩ ነው፡፡ ጧፍ በየእጁ ላይ ይንበለበላል፡፡ ችቦ ይተኮሳል! እጅግ ደማቅ መልክ ነው ያለው፡፡ ከታቦቱ ጀርባ የጉራጌ ባህላዊ እጀባ አለ፡፡ ድንጋያማ ቁልቁለት አለ፡፡ ለኔ ነው እንጂ አገሬውማ የለመደው ነው፡፡ ቃጭል፣ ሆታ፣ በቀለም የደመቀ ታቦት!  “ኤቦ” ይላል ያገሬው እጀባ ዜማ! ይሄኔ ባለቤቴና ሌሎች ወዳጆቻችን ከአዲሳባ መጡ፡፡ ደርሰውበታል ታቦቱን፡፡ ቅዳሴ ገቡ፡፡
 “ባለቤቱ ስትመጣ ዕውነተኛ ሳቅ ሳቀ” ብሎ ያሬድ የተባለ ወዳጃችን ቀለደብኝ፡፡ ሴቶች የበዙበት መዘምራን… የባህል ዜማና አገሬው… በአረንጓዴ የተከበበ ባለፀዳለ-ሞገስ ታቦት! እንግዲህ ዑደተ-ታቦቱ ሂደቱን ጨረሰ - ነገሠ! በመጨረሻ እርዳታ ያደረጉ ሰዎች ዝርዝር ተነበበ፡፡ ይገርማል፤ ሰው እጣን እዚያው ገዝቶ እዚያው ይለግሳል፡፡ ዕምነት ማለት ይሄ ነው! ዕሮብ ስለሆነ ቅዳሴ ተገባ! እኔ ወደማረፊችን ሄድኩ፡፡
ይቀጥላል

Published in ባህል