• ከአልሸባብና ደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል
  • መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል

         በጅሃድ ጦርነት እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም በጅማ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች፤ ሰሞኑን ፍ/ቤት ቀርበው ክሣቸው ከተሰማ በኋላ የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ባለፈው ረቡዕ ክሣቸው በንባብ የተሰማው 7 ተጠርጣሪዎች፡- ጃፋር መሃመድ መሃሙድ ኑር፣ መሃመድ ሣኒ፣ መህዲን ጀማል፣ መሃሙድ አባቢያ፣ አንዋር ትጃኔ እና ሼክ ከማል አባጪብሳ ሲሆኑ በዋና ወንጀል ፈፃሚነት መሠረታቸውን ጅማ አካባቢ አድርገው፣ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቁሟል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ የሽብር ቡድንና በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ጋር ግንኙነት ነበራቸውም ብሏል - የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ፡፡ 1ኛ ተከሣሽ ጃፋር መሃመድ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖታዊ ጦርነት ለማወጅና እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም የሚያስችለውን ስልጠና ከደቡብ አፍሪካ ወስዶ በመምጣት፣ ጅማ አካባቢ ለአላማው ማስፈፀሚያ ቦታ በመምረጥ አባላትን በመመልመል ሲንቀሳቀስ ነበር ተብሏል፡፡
ተከሳሹ በደቡብ አፍሪካ ይገኛል ከተባለው አሸባሪ ቡድን የተላከለትን 80ሺህ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ተቀብሎ ለመሣሪያ መግዣ እንደተጠቀመበት የክስ መዝገቡ አመልክቷል፡፡ በጅማ አካባቢ ኮዳ በተባለ ጫካ ውስጥ የመለመላቸው ግለሰቦች ለ6 ቀናት ስልጠና እንደወሰዱና እንቅስቃሴው በፀጥታ ኃይሎች እንደተደረሰበት ሲረዳ፣ ወደ ሶማሊያ ሄዶ ከአልሻባብ ጋር ለመቀላቀል ሙከራ ሲያደርግ በግንቦት 2006 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋሉን የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡
በመዝገቡ የተካተቱት ቀሪዎቹ 6 ተጠርጣሪዎች አባል በመሆን፣ የሽብር ተልዕኮ በመቀበልና እስላማዊ መንግስት የመመስረት አላማቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ በፈፀሙት በሽብር ቡድን ውስጥ የመሳተፍ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤቱ ክሱን በንባብ ካሰማ በኋላ፣ የተከሳሾች ጠበቃ በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለህዳር 10 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Published in ዜና

      ኢትዮጵያ ለአስር የደቡብ ሱዳን የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች (ሚኒስትር ዴኤታዎች) እና ለአስር የደቡብ ሱዳን የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች በአጠቃላይ ለሃያ ሰዎች በድህረ-ምረቃ ደረጃ ነፃ የትምህርት ዕድል ለመስጠት ስምምነት ያደረገችበትን ሰነድ የሚያፀድቅ ረቂቅ አዋጅ ቀረበ፡፡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጁ፤ ለትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል መጋቢት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በጁባ የተፈረመውና ሁለቱ አገራት በትምህርቱ ዘርፍ ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው የሚገልፀውን ስምምነት መሠረት አድርጐ የወጣው ረቂቅ አዋጁ፤ ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ከደቡብ ሱዳን መንግስት የተሻለ አቅም ያላት በመሆኑ በዘርፉ የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠትና ልምድ በማካፈል እገዛ ለማድረግ የተስማማች ሲሆን፤ ለሃያ የደቡብ ሱዳን የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ነፃ የትምህርት ዕድል እንድትሰጥ ተስማምታለች፡፡ ደቡብ ሱዳንን በትምህርት መርሃ ግብር ቀረፃ ለመደገፍ መስማማቷን ሰነዱ ያመለክታል፡፡
ስምምነቱ በየሀገራቱ የውስጥ አሠራር መሠረት ከፀደቀ በኋላ ለአምስት ዓመታት በሥራ ላይ እንደሚውል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የትብብር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ያመለክታል፡፡

Published in ዜና

        ለተለያዩ የቴሌኮሙኒኬሽን ሥራዎች የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን በህገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገቡ ተገኝተዋል የተባሉ 3 የውጭ አገር ዜጐችና አራት የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞችን ጨምሮ 70 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ አገሪቱን በሚሊዮን የሚገመት ገቢ አሣጥተዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች፤ በህገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ የተለያዩ ለቴሌኮሙኒኬሽን ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን በአዲስ አበባ፣ አዋሣ ጭሮ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረርና ጅግጅጋ ከተሞች ጥቅም ላይ አውለዋል ተብሏል፡፡ ፖሊስ፤ ተጠርጣሪዎቹ ህገወጥ ድርጊታቸውን በውጭና በሀገር ውስጥ በተደራጀ ሁኔታ ሲያከናውኑ እንደቆዩ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
ህብረተሰቡ በሚኖርበት አካባቢ ለየት ያሉ እንደ ትናንሽ የሳተላይት መቀበያ ያሉ የቴክኖሎጂ መጠቀሚያና መሰል መሣሪያዎች ተተክለው ሲያይ በየአካባቢያቸው ለሚገኝ የፖሊስ አካል ወይም ለኢትዮ ቴሌኮም ነጻ የጥሪ ማዕከል 994 በመጠቀም ጥቆማ ማቅረብ ይችላል ተብሏል፡፡

Published in ዜና

          ፖርትላንድ ፕሪቶሪያ ሲሜንት (ፒፒሲ) የተሰኘው ተቀማጭነቱ በደቡብ አፍሪካ የሆነ የሲሚንቶ አምራች ኩባንያ፣ በሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ውስጥ የነበረውን 27 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ወደ 51 በመቶ ማሳደጉን አስታወቀ፡፡
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ቤኪ ሲባያ ባለፈው ረቡዕ ለዴስቲኒ ኮኔክት ድረ ገጽ እንደተናገሩት፣ ከሁለት አመታት በፊት ከሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር 27 በመቶ የአክስዮን ድርሻ የገዛው ፒፒሲ፤ ድርሻውን ወደ 51 በመቶ ማሳደጉ፣ በአፍሪካ አህጉር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማጐልበት የቀየሰውን ስትራቴጂ የበለጠ ለማፋጠን አቅም ይፈጥርለታል፡፡
በ135 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ከአዲስ አበባ በ35 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ግንባታው በመከናወን ላይ የሚገኘው የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ከሁለት አመታት በኋላ ግንባታው ተጠናቆ የማምረት ስራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅና በአመት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንደሚኖረውም ሲባያ ተናግረዋል፡፡
ቀሪው 49 በመቶ የሃበሻ ሲሚንቶ የአክሲዮን ድርሻ ከ16 ሺ በላይ በሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ባለአክሲዮኖች ባለቤትነት እንደሚቀጥልም ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለው ገልጸዋል፡፡

Published in ዜና

    ለማዕከሉ የእንጨት መሰንጠቂያ ሊያቋቁም ቃል ገባ
መንግሥቱ አበበ
የዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዓለም ፍፁምና ባለቤታቸው ወ/ሮ ገነት ገበያ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል 500ሺ ብር ግምት ያለው ድጋፍ ማድረጋቸውን የማዕከሉ መሥራች ገለጸ፡፡
የማዕከሉ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ቢንያም በለጠ፤ ባለሀብቶቹ፣ የጥቅምት መድኀኒዓለም ዓመታዊ በዓልን ምክንያት በማድረግ፣ በማዕከሉ ለሚገኙ 700 ያህል አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን አንድ አንድ ጋቢ ያለበሱ ሲሆን በማዕከሉ ለተገኙ በርካታ እንግዶችም የተሟላ የምሳ እንዳደረጉ ተናግሯል፡፡
መቄዶንያ፣ ምንም የውጭ ፈንድና ቋሚ ገቢ እንደሌለውና አረጋውያኑንና ሕሙማኑን የሚንከባከበው የግል በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች በሚያደርጉለት ድጋፍ እንደሆነ ጠቅሶ ባለሀብቶቹ አቶ ዓለምና ወ/ሮ ገነት፤ መቄዶንያ፣ የራሱን ገቢ በመፍጠር ራሱን እንዲደጉም በማሰብ የእንጨት መሰንጠቂያ ድርጅት ለማቋቋም ቃል መግባታቸውን አስታውቋል፡፡ በጎ አድራጊዎቹ በዕለቱ ለምሳ ግብዣና ለአልባሳት ግዢ ያወጡት ወጪ 500,000 ብር እንደሚገመት አቶ ቢንያም ገልጿል፡፡
በየዓመቱ የጥቅምት መድኀኒዓለምን እቤታቸው ደግሰው ዘመድ ወዳጆቻቸውን በመጋበዝና የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ የሆኑትን በማብላት እንደሚዘክሩ የገለጹት አቶ ዓለም፤ ዘንድሮ  እኔና ባለቤቴ መቄዶንያ በማዕከል ሰብስቦ ዓመቱን ሙሉ የሚንከባከባቸውን አረጋውያንን  ለምን አንድ ቀን ምሳ አናበላም? በማለት ያዘጋጁት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንጨት መሰንጠቂያው አሁን በማዕከሉ ላሉት 700 ተረጂዎችና ወደፊትም ለሚጨመሩት ቋሚ ገቢ መፍጠሪያ ይሆናል የሚል ግምት የለኝም ያሉት አቶ ዓለም፤ “ምንም እንኳን እንደ ማዕከሉ ከዓመት ዓመት አዛውንቱን መደገፍ ባልችልም ማዕከሉ ለገቢ ማግኛ ብሎ ከቀረፃቸው ብዙ ፕሮጀክቶች አንዱ የእንጨት መሰንጠቂያ መሆኑን ሲነግሩኝ እኔም ፕሮጀክታቸውን ለመደገፍ ተስማማሁ፤ ስለዚህ እኔ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ አደርጋለሁ” ብለዋል፡፡
አቅመ ደካማና ሕሙማን ችግረኞችን ለመርዳት አንድ ሰው የግድ ሃብታም መሆን የለበትም፣ ሰው መሆን ብቻ ይበቃል ያለው ቢንያም፤ “ዕርዳታ ሲባል በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በዓይነትም ይቻላል፡፡ ያለው በገንዘቡ፣ የሌለው ደግሞ በጉልበቱ፣ በሙያውና በእውቀቱ ሊረዳ ይችላል፡፡ በማዕከሉ ውስጥ ገንዘብ ሳይከፈላቸው በጉልበትና በሙያቸው የሚረዱ 150 በጐ ፈቃደኞች” አሉ ብሏል፡፡
አሁን ማዕከሉ ለአቅመ ደካማ አረጋውያንና ለአዕምሮ ሕሙማን የሚያደርገውን ድጋፍ፣ መንግሥትም እያየና እያደነቀ ብቻ ሳይሆን እየደገፈም ነው፤ የተረጂዎቹ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ በ40 ሰዎች ጀምረን አሁን 700 ደርሰናል፡፡ በቅርቡም 200 ተረጂዎችን ለመጨመር አቅደናል፡፡ በወላጆቼ ግቢ ጀምረን እሱ ሲሞላ ወደ ጐረቤት ተሸጋገርን፡፡ አሁን 4ኛ ግቢ ሞልተን 5ኛ ጀምረናል፡፡
“የቦታ ጥበት እንዳለብን የተረዳው መንግሥት 30ሺ ካ.ሜ ቦታ ፈቅዶልን ለመረከብ ብዙ ሂደት አልፈናል - የካቢኔው ውሳኔ ብቻ ነው የቀረን፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ማኅበራዊ ቢሮና የከተማዋ አስተዳደር ላደረጉልን ከፍተኛ ትብብር በተረጂዎቹ ስም በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በየመንገዱ የወደቁትን የምናነሳው የኢፌዲሪ በጐ አድራጐትና ማኅበራዊ ኤጀንሲ በሰጠን መኪና ነው፡፡ እሱንና አንበሳ የከተማ አውቶቡስን በጣም እናመሰግናለን፡፡ እነዚህ የመንግሥት ተቋማት ስለሆኑ ጠቀስኩ እንጂ፤ እስካሁን ሲረዱን የቆዩት የግል ደርጅቶችና በጐ አድራጊ ግለሰቦች በርካታ ናቸው፡፡ እነሱን መዘርዘር ከባድ ስለሆነ፣ ሁሉንም በደፈናው በጣም አመሰግናለሁ” በማለት አስረድቷል የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ቢንያም በለጠ አዲስ፡፡
ወ/ሮ መሠረት ረጋሳና አቶ ብርሃኑ ታደሰ፣ የሠርጋቸውን ሥነ-ሥርዓት የሚፈጽሙት እዚያ ባይሆንም ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ያላቸውን ክብር ለመግለጽ ወደ መቄዶንያ ማዕከል ጐራ ብለው የአረጋውያኑን ጉልበት ስመው ተመልሰዋል፡፡


Published in ዜና

    የአመራር አባላት ድብደባና እስር እየደረሰባቸው ነው አለ

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የአንድነት ፓርቲ አዲሱን ስራ አስፈፃሚ አላውቀውም በማለት ፓርቲውን ወክሎ እንዳይንቀሳቀስ ማገዱ በአመራሩ ዘንድ ግራ የመጋባት ስሜት ፈጥሯል፡፡  ፓርቲው ቦርዱን ማብራሪያ እንደሚጠይቅ ገልጿል፡፡
የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ተጠባባቂ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃም ስለ ሁኔታው ለአዲስ አድማስ ሲያብራሩ፤ “ኢ/ር ግዛቸው በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ አዲሱ ስራ አስፈጻሚ የተመረጠው በተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ነው” ብለዋል፡፡
በተሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ጠቅላላ ጉባኤው በማይኖርበት ወቅት ፕሬዚዳንት የመምረጥን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን ብሄራዊ ምክር ቤቱ ውክልና ተሰጥቶታል ይላሉ፤ ኃላፊው፡፡ መተዳደሪያ ደንቡን ለምርጫ ቦርድ ካስገባን ከወር በላይ ሆኖታል ያሉት አቶ አስራት፤ በቦርዱ ደንብ መሰረት፣ አንድ ፓርቲ ያሻሻለውን መተዳደሪያ ደንብ ለቦርዱ ባስገባ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካልተሰጠው ደንቡን እንደተቀበለው ይቆጠራል፤ በዚህ መሰረት መስተናገድ አለብን፤ ይሄንንም ለቦርዱ እናሳውቃለን ብለዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት አዲሱን የአንድነት አመራር ባገደበት ደብዳቤው፤ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ተሻሽሏል ተብሎ ለቦርዱ የቀረበው ደንብ የተለያዩ ጉድለቶች ስላሉበት እውቅና እንዳልሰጠው ጠቅሶ ደንቡ እውቅና ሳያገኝ ፕሬዚዳንቱን ከኃላፊነት ማንሳት ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡ አዲሱ አመራር ቦርዱ የመጨረሻውን ውሣኔ እስኪሰጥ ድረስም ፓርቲውን ወክሎ መንቀሳቀስ እንደማይችል የቦርዱ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ፓርቲው በትናንትናው እለት በፅ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በፓርቲው የአመራር አባላት ላይ ድብደባና እንግልት እንዲሁም እስር እየተፈፀመባቸው መሆኑን አስታውቆ፤ ድርጊቱ ገዥው ፓርቲ አንድነትን ለማዳከም ከከፈታቸው ዘመቻዎች አንዱ ነው ብሏል፡፡ ኢህአዴግ አካሄዱን ቆም ብሎ እንዲያስብም ፓርቲው ጠይቋል፡፡  

Published in ዜና

ማረጥ በየትኛዋም ሴት ላይ ሊከሰት የሚችል ተፈጥሮአዊ ክስተት ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እንደ አንድ የጤና እክል ሲቆጥሩት ይስተዋላል፡፡ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ፈፅሞ የተሳሳተና ከሳይንሰዊ እይታ ውጪ የሆነ ነው፡፡
 በዛሬው ፅሁፋችን እውን ማረጥ ተፈጥሮአዊ ነው ወይንስ ጥቂቶች እንደሚሉት የጤና እክል ነው? የሚለውን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡ NIA (National Institute On Aging) መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ የጤና ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡
ማረጥ ምንድነው?
የአንዲት ሴት የማረጫ አማካኝ እድሜ ስንትነው?
ከማረጧ በፊት እንዲሁም በኋላስ ምን አይነት የጤና እክሎች ይገጥሟታል? የሚሉትን ጉዳዮች አስመልክቶ ያወጣውን ፅሁፍ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡-
ማረጥ ምንድነው?
ማረጥ ልክ እንደ ጉርምስና ሁሉ በተወሰነ የእድሜ ክልል ላይ የሚከሰት ተፈጥሮአዊ ክሰተት ነው፤ ይህ ተፈጥሮአዊ ክሰተት የወር አበባ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ ሆርሞኖች     መጠን መቀነሱን ተከትሎ የወር አበባ ሲቆም የሚፈጠር ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አከላዊ እንዲሁም ስነልቦናዊ ለውጦች ይኖራሉ፡! በለውጡ ሶስት ደረጃዎች ይከሰታሉ፡፡
ከማረጥ በፊት፣
በማረጥ ወቅት እንዲሁም
ከማረጥ በኋላ፡፡
አብዛኛዎቹ ለውጦች አንዲት ሴት ወደ ማረጫ የእድሜ ክልል ስትቃረብ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በሰውነቷ ውስጥ የሚገኘው የኤስትሮጅንና ፕሮጀስትሮን ሆርሞን ስለሚቀንስ በተለያየ የሰውነት ክፍሎች ላይ የተለያዩ ለውጦች ይታያሉ፡፡
 በመቀጠልም የወር አበባ መታየቱን ያቆማል፡፡ ይህም ለማረጧ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ከማረጥ በኋላ ያሉ ለውጦችም የሚከሰቱት ከዚህ በኋላ ነው፡፡ብዙሀኑ ሴቶች እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርሱት በሀምሳዎቹ መጀመሪያ ባለው የእድሜ ክልል ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ከዚህ ቀደም ብለው በአርባዎቹ መጀመሪያ ወይም ደግሞ ዘግይተው በሀምሳዎቹ መጨረሻ ባለው ጊዜ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከተገለፀው አማካኝ የእድሜ ክልል ቀድመው ለማረጥ ተያያዥ ምክንያት ይሆናሉ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ሲጋራ ማጨስ እንዲሁም በማህፀን ላይ የተደረገ የቀዶ ጥገና በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ምልክቶቹ፡-
ሴቶች ወደዚህ የእድሜ ክልል ሲገቡ በሰውነታቸው ያለው የኤስትሮጅንና ፕሮጀሰትሮን መጠን በጣም ስለሚቀንስ የተለያዩ ምልክቶችን ማየት ይጀምራሉ፡፡ የሚከተሉት ዋናዋናዎቹ ናቸው፡-
1.    የወር አበባ የሚመጣበት ቀናት በእጅጉ         መቀራረብ፣
2.    የወር አበባ መጠን መጨመር፣
3.    በሰውነት ላይ የሚወጣ ሽፍታ፣
4.    የወር አበባ ከአንድ ሳምት በላይ መቆየት፣
5.    የወር አበባ ከቆመ ከአንድ አመት በኋላ ተመልሶ ሊታይ ይችላል  
ከላይ የተጠቀሱት አንዲት ወደዚህ የእድሜ ክልል መዳረሻ ላይ ያለች ሴት የሚያጋጥሟት ምልክቶች ሲሆኑ በምታርጥበት ወቅት ደግሞ ሌሎች በሰውነቷ ውስጥ ያለው የኤስትሮጅንና ፕሮጀስትሮን መጠን መቀነስ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አከላዊ ብሎም ስነልቦናዊ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ ተከታዮቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
1.    ድንገተኛና በተደጋጋሚ የሚከሰት የሰውነት         ሙቀት መጨመር፣
ይህም የሚከሰተው በሰውነታችን ያለው የኤስትሮጅን መጠን መቀነስ ጋር ተያይዞ ሲሆን አንዲት ሴት ካረጠች በኋላም ለተወሰኑ አመታት ሊቀጥል ይችላል፡፡ ይህ ድንገተኛ የሆነ የሰውነት ሙቀት ከፍ ማለት በይበልጥ በላይኛው የሰውነታችን ክፍል ማለትም በጀርባ፣ በአንገት እንዲሁም በፊት አካባቢ ይከሰታል፡፡ በአብዛኛውም ከ30 ሰኮንድ እስከ 10 ደቂቃ ሊቆይ ይችላል፡፡
2.    ብልት አከባቢ መድረቅ እንዲሁም የኢንፌክሽን መፈጠር ይህም ለወሲብ ፍላጎት መቀነስ ምክንያት ይሆናል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ አንዳንድ ሴቶች የሽንት መቋጠር ችግርም ያጋጥማቸዋል፡፡
3.    እንቅልፍ ማጣት፣ በማረጥ የእድሜ ክልል         ላይ ያሉ ሴቶች በአብዛኛው በቶሎ እንቅልፍ         ለመተኛት እንዲሁም እረዥም ሰአት         ለመተኛት ይቸገራሉ፡፡
4.    የወሲብ ፍላጎት መቀነስ፣
5.    ድብርት፣ የስሜት መለዋወጥ፣ መነጫነጭ         እንዲሁም ጭንቀት፡፡ በዚህ ወቅት             የተለመዱ     የባህሪ ለውጦች ናቸው፡፡    
6.    የሰውነት ክብደት መጨመር፣ የማስታወስ         ችሎታ መቀነስ፣ እንዲሁም ከአጥንት እና         መገጣጠሚያ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊከሰቱ         ይችልሉ፡፡
ለችግሮቹ መፍትሄ፡-
ማንኛዋም ሴት ቀደም ሲል የተጠቀሱትን አካላዊ እንዲሁም ስነልቦናዊ ችግሮች ሲገጥሟት የማረጥ ምልክቶች ሊሆን እንደሚችል በመገንዘብ የተለያዩ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይኖርባታል፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ግን ማረጥ እንደማንኛውም ተፈጥሮአዊ ክስተት ጊዜውን ጠብቆ ሊከሰት እንደሚችል ከዛም ጋር ተያይዞ ስለሚከሰቱ የጤና እክሎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ፅሁፉ በማረጥ ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ያስችላሉ ብሎ የሚከተሉትን ነጥቦች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ከሲጋራ እንዲሁም ከሌሎች እፆች መጠበቅ፣
የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርአትን መከተል፣ የቅባት ምግቦችን መቀነስ፣ በአንፃሩ ከፍተኛ የፋይበር መጠን ያላቸውን ምግቦች እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ አዘውትሮ መመገብ፣
በተጨማሪም ሰውነታችን በቂ የሆነ ካልሲየም፣ ቫይታሚን ዲ፣ ሌሎች ቫይታሚኖችን እንዲሁም ሚኒራል እያገኘ መሆኑን ማረጋገጥ፣
የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር፣
የሰውነት ሙቀት ከፍ ማለት ሲያጋጥም ሳሳ ያሉ ልብሶችን መልበስ እንዲሁም ቀዝቃዛና ነፋሻማ በሆኑ ቦታዎች መቀመጥ፣
    ከላይ ከተገለፁት በተጨማሪም ለዘወትር         ሊታወሱ     ይገባል ብሎ ፅሁፍ ተከታዮቹን         ነጥቦችም     አስፍሯል፡-
ከደም ግፊት፣ ከኮለስትሮል እንዲም ከሌሎች የጤና እክሎች ጋር በተያያዘ በሀኪም የታዘዙ መድሀኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፣
ብልት አከባቢ መድረቅ እንዲሁም የኢንፌክሽን መፈጠር ጋር በተያያዘ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መድሀኒት እንዲሁም የተለያዩ ቅባቶችን መጠቀም፣
በጡት አካባቢ ማበጥ እና ሲነካካ መጠጠር ሲያጋጥም ሀኪም ጋር ቀርቦ  አስፈላጊውን የህክምና ክትትል  ማድረግ፣ማረጥ የህክምና ክትትል በማድረግ ሊወገድ የሚችል የጤና እክል አይደለም፡፡ ነገር ግን የተለየ የጤና እክል በተለይም ተደጋጋሚ የሆነ ድንገተኛ የሰውነት ሙቀት መጠን ሲያጋጥም የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

የሰውነት ሙቀት ከፍ ማለት ሲኖር፡-
ቀዝቃዛና ነፋስ ያለበት ቦታ መቀመጥ፣
ሳሳ ያሉና  ከሰውነታችን የሚወጣውን ሙቀት ማስወጣት የሚችሉ ልብሶችን መልበስ፣
ቀዝቃዛ መጠጦች መውሰድ ይመከራል፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

           አንድ የሙያ ባልደረባዬ ባለፈው ሳምንት ስልክ ይደውልልኝና “የአንድ የፍቅር ደብዳቤ አውደ ርዕይ ተከፍቷልና ብትጐበኚው ምን ይመስልሻል” አለኝ፡፡ የፍቅር ደብዳቤ አውደ ርዕይ የሚባል ሰምቼም አጋጥሞኝም ስለማያውቅ፣ ነገሩ ትንሽ ግር ቢለኝ ከባልደረባዬ ማብራሪያ ጠየቅሁ፡፡ ከዚያበቀጥታ ከደብዳቤዎቹ ፀሐፊ ጋር በመደዋወል ቀራኒዮ መድሃኒያለም አካባቢ ወደሚገኘው የፍቅር ደብዳቤ አውደ ርዕይ ነው ያመራሁት፡፡ አጃኢብ ነው እናንተዬ፤ እንዲህም አለ እንዴ ስል ራሴን ጠየቅኩኝ፡፡ መቼም በምድር ላይ እንዲህ አይነት ብዛትና ጥልቀት ያለው ደብዳቤ የተፃፈላት የመጀመሪያዋ ይህቺ ሴት እንደምትሆን ገመትኩ፡፡
በ1984 ዓ.ም ገደማ የአቶ ስዩም ገ/ፃዲቅ የቅርብ ጓደኛ የሆነ ሰው ሐረር፣ ጨለንቆ የተባለ ከተማ ውስጥ በቀያሽነት ይሰራል፡፡ የዚህ ሰው እጮኛ በወቅቱ ሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ትሰራ ነበር፡፡ ታዲያ ሀረር ጨለንቆ የሚሰራው ጓደኛው ጂዳ ለምትገኘው እጮኛው የረቀቀ የፍቅር ደብዳቤ አይደለም የሰላምታ ደብዳቤ ጽፎ ወደ ጂዳ ለመላክ ጨርሶ አይመቸውም፡፡ በቦታውም በስራውም ምክንያት፡፡ ይህንን የጓደኛውን ችግር የተረዳው አቶ ስዩም፤ ጓደኛውን በመወከል ለጓደኛው እጮኛ የተከሸኑ የፍቅር ደብዳቤዎችን እየፃፈ መላክ ይጀምራል፡፡ ደብዳቤዎቹ ከትውልድ አገሩና ወገኑ በብዙ ማይል ርቀት ላይ ለሚገኝ ስደተኛ የአዕምሮ ምግብ፣ የልብ፣ መጽናኛ፣ ብርታትና ጉልበት ስለሚሆኑ ይህቺ ልጅ የስዩምን ደብዳቤ በየሁለት ሳምንቱ በጉጉት ትጠብቅ እንደነበር አውደ ርዕዩን የከፈተው የደብዳቤዎቹ ፀሐፊ አቶ ስዩም ገ/ፃዲቅ አጫውቶኛል፡፡
እንኳን ደብዳቤው የሚላክላት ሴት ሌሎችም ኢትዮጵያውን ሴት ጓደኞቿ ደብዳቤውን ተሰባስበው የማንበብ ልምድ ስለነበራቸው በጉጉት ሚጠብቁት ነገር ነበር ይላሉ፡፡ አቶ ስዩም ይሄን ከሰሙ በኋላ ነው ለሴቶቹ አንድ ጥያቄ ያቀረቡት፡፡ “እንዲህ አይነት ደብዳቤ እንዲፃፍላት የምትፈልግ ሴት ከመሃላችሁ ካለች በሰንጠረዥ ሰርቼ የምልከውን ጨዋታ በትክክል ሰርቶ የላከ አሸናፊ ይሆናል፤ ከዚያም ሽልማት የሚሆን ደብዳቤ ይላክለታል” በማለት ፈተናውን ላኩላቸው” ይላሉ አቶ ስዩም፡፡ ከእነዚህ በርካታ ሴቶች  መካከል ገነት ጥጋቡ ክብረቴ የተባለች ሴት ብቻ ሰንጠረዡን በትክክል ሰርታ መገናኘት ያለባቸውን ቁጥሮች አገናኝታ አሸናፊ ሆነች፡፡ ያቺ ሴት የዛሬዋ የአቶ ስዩም ገ/ፃዲቅ የትዳር አጋር ሆና ላለፉት ሰባት ዓመታት በትዳር አብራቸው ዘልቃለች፡፡ እሷ ሳዑዲ አረቢያ እየሰራች በነበረችበት ከ1988 እስከ 1994 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ስድስት አመታት የተፃፉላት ልብ አቅላጭ የፍቅር ደብዳቤዎች ናቸው ለህዝብ እይታ የቀረቡት አጃኢብ ነው፡፡
“ከ1986 እስከ 1988 ዓ.ም ድረስ እኔና ገንዬ በሶስተኛ ወገን ማለትም በጓደኛዬ እጮኛ በኩል ስንፃፃፍ የቆየነው የተራ ጓደኝነት ዓይነት ደብዳቤ ነበር ይላሉ፡፡ አቶ ስዩም፡፡ ሆኖም የጓደኛው እጮኛ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ፣ አግብቶ እንደሆነ፣ እጮኛ ይኖረው እንደሆነ በመጠየቅ ነፃ መሆኑን ስታውቅ ለምን ከገኒ ጋር የፍቅር ግንኙነት አትጀምሩም በማለት እንደጠየቀችው  የሚያስታውሰው አቶ ስዩም፤ የገነትን ፈቃደኝነት ካረጋገጠ በኋላ ገና ሳይተያዩ በደብዳቤ ብቻ ወደ ፍቅር መግባታቸውን አጫውቶኛል፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ አፍሪካ ህብረት አካባቢ ተወልደው ያደጉት አቶ ስዩም፤ ለስነ - ፅሁፍ ትልቅ ፍቅር እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡ በአይንህ ያላየሃትን ሴት ምርጫህ ትሁን አትሁን ሳትለይ በደብዳቤ ብቻ ወደ ፍቅር ግንኙነት መግባት አይከብድም በማለት ጠየቅኋቸው፡፡ “እኔ ሁሌም መልክና ቁመና አስደንቆኝ አያውቅም፤ ገንዬ በሶስተኛ ወገን ስንፃፃፍ የምትልክልኝ ደብዳቤዎች በሳልና አስተዋይ መሆኗን ከደብዳቤዋ መረዳት ችዬ ነበር፡፡ ለእኔ ደግሞ ይሄ በቂ ነበር” ነው ያለኝ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ለስድስት ተከታታይ አመታት ደብዳቤዎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ጐረፉ፡፡ የፍቅር ንፋስ እያከነፈ ጂዳ የሚያደርሳቸው እነዚህ ምህታታዊ ደብዳቤዎች መልስ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፤ ብዛታቸው ወደ ጂዳ የሚሄደውን ያህል ባይሆንም፡፡
የደብዳቤዎቹ አይነቶች
በጣም የሚገርመው የደብዳቤዎቹ ብዛት ከሁለት መቶ በላይ መሆኑ ወይም፤ በአማረ የእጅ ጽሑፍና በምርጥ ቃላት መከሸናቸው አይደለም፡፡ በጣም አፍዞና አደንግዞ የሚያስቀረው ደብዳቤዎቹ ሳይሰለቹ እንዲነበቡ የሚዘጋጁበት የወረቀት ቅርፅ፣ ቀለምና መጠን ነበር፡፡ ደብዳቤዎቹን የማሳያችሁ በምስል ቢሆን እንዴት ደስ ባለኝ፡፡ በጣም ትንሽ መጠን ያላት ደብዳቤ የአንድን ሰው ግማሽ መዳፍ ታክልና በልብ ቅርፅ ተሰርታ፤ በሮዝ፣ በቢጫና በነጭ የወረቀት ቀለሞች የተዘጋጀች ስትሆን፣ 32 ገፆችን አካታለች፡፡ ትልቁ መቶ ገጽ ያለው ደብዳቤ ደግሞ በተለያየ ቅርጽ በተቆረጡና ደብዳቤዎች ሶስት አይነት ቀለም ባላቸው ወረቀቶች የተዘጋጀ ነው፡፡ ሶስት ሜትር ርዝመት ያለው ደብዳቤ፤ አጃኢብ ከሚያሰኙት አንዱ ሲሆን ወረቀት ተቀጣጥሎ በኡሁ እየተጣበቀ ነው ያን ያህል የረዘመው፡፡ ደብዳቤው ግን አንድ ወጥ ነው፡፡ በልብ ቅርፅ፣ በብሮሸር መልክ፣ በእንቁላል ቅርጽ፣ በክብ፣ በአበባ መልክ ተቀርፀው የተዘጋጁት ደብዳቤዎችም እንደትንግርት የሚታዩ ናቸው፡፡
ቀራኒዮ መድሃኔዓለም ከአይመን ህንፃ ገባ ብሎ ባለው መንደር ውስጥ የተከፈተው ይሄው አውደ ርዕይ፤ ገና ወደ ግቢ ሲገባ በረጃጅም ሰንበሌጥና በተለያዩ የሳር አይነቶች የተከበበ ሲሆን የአንድ አርሶ አደር ግቢ የገቡ ስለሚመስለዎት በዛፉና በለምለሙ ሳር መንፈስዎ ይታደሳል፡፡ ደብዳቤዎቹ በሰባት ረድፍ ተደርድረዋል፣ በወቅቱ ደብዳቤዎቹን ለመላክ አቶ ስዩም ይጠቀምባቸው የነበሩ ቴምብሮች፣ ፖስት ካርዶችና መላኪያ ፖስታዎቹም ጭምር የአውደ ርዕዩ አካል ናቸው፡፡ አቶ ስዩም ሌላው ቀርቶ የእግሩን ቅርፅ በወረቀት ቀርፆ በማውጣት እዚያ ላይ የፍቅር ደብዳቤ ፅፎ ልኮላታል፡፡ “ይህ የሚወዱትን ሰው ለማግኘት እግር እስኪቀጥን መሄድን ያመለክታል” ብለዋል፡፡
ለመሆኑ ይህን ሁሉ ደብዳቤ በምን ጊዜሽ ታነቢዋለሽ? ለሚፃፍልሽስ ደብዳቤ መልስ የመፃፍ ልምድ ነበረሽ ወይ ስል ወ/ሮ ገነትን ጠየቅኋት፡፡ ጐንደር ውስጥ አዲስ ዘመን የሚባል ከተማ ተወልዳ ያደገችውና አጐቷ ጋር ለመኖር ወደ አዲስ አበባ እንደመጣች ያጫወተችን የአቶ ስዩም ባለቤት፣ ከዚያም እህቷ ጅዳ እንደወሰደቻት ገልፃ፣ ስዩምን በጓደኛዋ በኩል እንደተዋወቀችው ነግራኛለች፡፡ “እኛ ለጓደኛችን የሚፅፍላትን ደብዳቤ እናነባለን፤ እረፍት ወጥተን የሚልከውን ደብዳቤ እስከምናነብም እንቸኩል ነበር” የምትለው ወ/ሮ ገነት፣ በቀጥታ ለእኔ መፃፍ ከጀመረ በኋላ እረፍት ስወጣ ዋናው ስራዬ የእሱን ደብዳቤ ማንበብና ለእሱ ምላሽ መፃፍ ነበር” ብላለች፡፡ “እኔ መልስ የምፅፈው ስለጤንነቴ፣ ስለ ስራዬና አሰሪዎቼ፣ ስለኑሮና ጓደኞቼ ስለሚጠይቀኝ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት እንጂ እንደ እሱ ረቀቅ ያለ ደብዳቤ መፃፍ አልችልም በማለት አክላለች፡፡
በእያንዳንዱ ደብዳቤ ላይ ምክር አዘል፣ ለፍቅር ማጠናከሪያነት የሚያገለግሉ፣ ስለ ትዳር ክቡርነትና ስለታማኝነት የሚገልፁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተካትተዋል፡፡
በእያንዳንዱ ደብዳቤ ጀርባ ወይም ፊት ለፊት ላይ በረቀቀ አፃፃፍ “ገስ” የሚል ፅሑፍ ይታያል የገነትና የስዩም የመጀመሪያ ፊደሎች ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ደብዳቤ ላይ “ገኒዬ እወድሻለሁ” የሚለውም ቃል አይቀርም፡፡ አንዱ ደብዳቤ ሶስት ሜትር ከ28 ሳ.ሜ ርዝመት ያለው ሲሆን በጀርባውም በፊት ለፊቱም ፅሁፍ አለው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አውደ ርዕዩን ምሁራን፣ የስነ-ፅሁፍ ሰዎች፣ ተማሪዎች፣ እየጎበኑት ይገኛሉ፡፡
“ቦታውን ቀራኒዮ ነው ስትያቸው እንደ እውነተኛው ቀራኒዮ ሩቅ አድርገው ይስሉታል፤ በዚህ ምክንያት በጣም ብዙ ሰው ሊጎበኘው ሲችል እየጎበኘው አይደለም” የሚሉት አቶ ስዩም፤ በአሁኑ ሰዓት እነዚህ ደብዳቤዎች የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትም ጭምር ስለሆኑ በደንብ እንዲጎበኙና በግልፅ እንዲታዩ ከፖስታ ድርጅት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል፡፡ “ለመሆኑ ከ1994 እስከ 2000 ዓ.ም ባሉት አመታት እንዴት መፃፍ አቆሙ?” የሚል ጥያቄ አንስቼላቸው ነበር፡፡ “እውነት ነው በእነዚህ ዓመታት በጣም አልፎ አልፎ ብፅፍም ሙሉ ለሙሉ ግን አቁሜ ነበር ማለት እችላለሁ ምክንያቱ ደግሞ ቴክኖሎጂው ተንቀሳቃሽ ስልክን ፈጠረና ከገኒ ጋር በየጊዜው መደዋወልና ሃሳባችንን መለዋወጥ ጀመርን” ብለዋል አቶ ስዩም፡፡ ከዚያ ለኢትዮጵያ ሚሌኒየም መጥታ ተጋባን፤ ይሄው በትዳር ሰባት ዓመታትን አስቆጠርን፤ በሰላምና በፍቅር እየኖርን ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡ እርግጥ ነው ልጆች አላፈሩም፤ ምክንቱን ጠይቄው እኛ ፈጣሪን ጠይቀናል፤ ምላሽ እየጠበቅን ነው፡፡ ባይሳካም ዋናው ፍቅራችን ስለሆነ እንደችግር አንቆጥረውም፤ እነዚህ ደብዳቤዎች ልጆቻችን ናቸው በማለት መልሰዋል፡፡
ወ/ሮ ገነት በበኩሏ “ስዩም መልካም ባል ነው፤ በተለይ አረብ አገር እያለሁ እሱን ከተዋወቅሁ በኋላ በሚፅፍልኝ ምክር፣ አፅናኝ ቃላት፣ በሚሰጠኝ ፍቅር ብርታትና ጉልበት አግኝቼ ስራዬን በጥንካሬና በብቃት አጠናቅቄ እንድመጣ ረድቶኛል” ስትል ስለባሏ ያላትን አስተያየት ሰንዝራለች፡፡
“በአሁኑ ሰዓት በእነዚህ ደብዳቤዎች ላይ ጥናት እየሰራሁ ነው” የሚለው አቶ ስዩም፤ ትልልቅ ምሁራን ከጎበኙት በኋላ ለምርምር፣ ለማስተማሪያነትና ለመሰል አገልግሎቶች ይውላል እንዳሉት ገልፆ፣ ምን ያህል ቃላትን እንደተጠቀምኩ፣ ስሟንና እወድሻለሁ የሚለውን ለስንት ጊዜ እንደፃፍኩ፣ ምን ያህል ወረቀትና ገፆች እንደተጠቀምኩና መሰል ሁነቶችን የሚገልፅ ወደ 80 ገፅ የሚጠጋ ፅሁፍ ፅፌያለሁ፤ ግን ይቀረኛል በማለት አብራርተዋል፡፡ ምሁራን በሰጡኝ ጥቆማ “ጊነስ ቡክስ ኦፍ ሬከርድስ” ላይና በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በጉዳዩ ዙሪያ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ለመምከር አቅጃለሁ ከዚያ በፊት ግን ግልፅና አማካይ የሆነ ቦታ ላይ አውደ ርዕዩን ለህዝብ ክፍት ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ነኝ ሲልም ተናግረዋል፡፡
አውደ ርዕዩን ጎብኝተው አግራሞታቸውንና አድናቆታቸውን ከቸሩት ውስጥ “የጉንጉን” እና የየወዲያነሽ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር መርከብ መኩሪያ ይገኙበታል፡፡
አቶ ስዩም ወ/ፃዲቅ አፍሪካ ህብረት ሳር ቤት አካባቢ ተወልደው ያደጉ ሲሆን በፍሬህይወትና በሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤቶች ተምረው 12ኛ ክፍልን ካጠናቀቁ በኋላ በኢትዮጵያ አየር ሃይል ውስጥ በግራውንድ ቴክኒሺያንነት ለሰባት አመታት አገልግለዋል፡፡ በሬዲዮ ኤሌክትሮኒክስ ስራ አስመራ ውስጥ ለሁለት አመታት መስራታቸውንም አጫውተውኛል፡፡ በተለያዩ የመንግስት ስራዎች ከሰሩ በኋላ በመንግስት ለውጥ ጊዜ ስራቸውን ለቀው አሁን ከጓደኞቻቸው ጋር “ፍኖት የማስታወቂያ እና ህትመት ስራ ድርጅትን” በመክፈት በግል እየሰሩ ሲሆን የሲኒማና የፎቶግራፍ ትምህርት ማስተር ት/ቤት ተምረው ተመርቀዋል፡፡ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ የተዋወቋን ፍቅረኛቸውን አግብተው በመኖር ላይ ሲሆኑ የተዋወቁበትን 20ኛ ዓመት አስመልክተው ከሐምሌ 19 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ይህን የደብዳቤ አውደ ርዕይ ከፍተው በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡   

Published in ጥበብ

በመጪው ጥር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይደረጋል
ከደ/አፍሪካው ዴክለርክ በኋላ የመጀመሪያው ነጭ አፍሪካዊ መሪ ናቸው

        ዛምቢያን ላለፉት ሶስት አመታት ያህል ያስተዳደሩት ፕሬዚዳንት ሚካኤል ሳታ፤ ባለፈው ማክሰኞ በ77 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ፣ አገሪቱ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በነጭ ጊዜያዊ መሪ መተዳደር መጀመሯን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ለንደን ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምናቸውን ለሳምንታት ሲከታተሉ የቆዩት ሳታ መሞታቸውን ተከትሎ  የዛምቢያ መንግስት ምክር ቤት በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በአገሪቱ ህገመንግስት በተቀመጠው መሰረት በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማካሄድን ጨምሮ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በሚደረግበት ሁኔታ ላይ የመከረ ሲሆን፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሰሩ የቆዩትን ጋይ ስኮት ጊዜያዊ መሪ አድርጎ መርጧል፡፡
ሟቹ ፕሬዚዳንት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለህክምና ወደ እንግሊዝ ሲሄዱ፣ አገሪቱን በተጠባባቂነት የመምራቱን ሃላፊነት ለመከላከያ ሚኒስትሩ ኤድጋር ሉንጉ ሰጥተው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ሞታቸውን ተከትሎ ግን፣ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫ እስከሚካሄድና አዲስ ፕሬዚዳንት እስኪመረጥ ድረስ፣ ጋይ ስኮት አገሪቱን በጊዜያዊነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡እ.ኤ.አ በ2001 “ፓትሪዮቲ ፍሮንት” የተባለውን ፓርቲ በመቀላቀል በወቅቱ በተካሄደው ምርጫ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ተመርጠው ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ የስኮትላንድ ዝርያ ያላቸውና ወላጆቻቸው ከዛምቢያ ውጭ የተወለዱ በመሆናቸው የአገሪቱ ህገመንግስት ስለሚከለክላቸው በመጪው ጥር በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ላይሳተፉ እንደሚችሉም ገልጿል፡፡
የ60 አመቱ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ምሩቅ ጋይ ስኮት፣ ከደቡብ አፍሪካው መሪ ዴክለርክ በኋላ አንድን የአፍሪካ አገር ለመምራት የቻሉ የመጀመሪያው ነጭ መሪ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡
ሟቹ ፕሬዚዳንት ሳታ ላለፉት አራት ወራት ከአደባባይ መራቃቸውን ተከትሎ፣ የከፋ ህመም ላይ ወድቀዋል የሚል ወሬ በስፋት ሲናፈስ መቆየቱን ዘገባው አስታውሶ፤ ፕሬዚዳንቱ በመስከረም ወር አጋማሽ በተከናወነው የአገሪቱ ፓርላማ የመክፈቻ ስነስርአት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ የከፋ የጤና ችግር ላይ ናቸው በሚል በስፋት የተሰራጨውን ወሬ በተመለከተ ዘና ያለ ምላሽ ሰጥተው ነበር - “እስካሁን አልሞትኩም” በማለት፡፡ከዚህ የመክፈቻ ስነስርዓት በኋላ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኒውዮርክ ጽህፈት ቤት ሊያደርጉት የነበረው ንግግር መሰረዙን ተከትሎ በአሜሪካ ባረፉበት ሆቴል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው እንደነበር ፖሊስ አስታውቶ ነበር፡፡የአገሪቱ መንግስት ፕሬዚዳንቱ በውጭ ሃገር እየታከሙ እንደሚገኙ ከመግለጽ ባለፈ፣ የት አገር እንደሚገኙ ሳይጠቁም መቆየቱንና የዛምቢያ ተቃዋሚ ቡድኖችም ፕሬዚዳንቱ አገሪቱን የመምራት ብቃት እንደሌላቸው ሲናገሩ እንደነበር ዘገባው አስታውቋል፡፡
የተባ አንደበት ባለቤት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በአገሬው ዘንድ ‘ንጉስ ኮብራ’ በሚል የቅጽል ስም የሚጠሩትና በተቃዋሚ ፓርቲ አባልነት ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ተወዳድረው በ2011 ስልጣን የያዙት አምስተኛው የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ሳታ፤ ታጋሽነት የሚጎላቸው መሪ ናቸው” በሚል ሲተቹ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ፕሬዚዳንቱን ለሞት የዳረጋቸው ህመም ምን እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Monday, 03 November 2014 09:10

የፍቅር ጥግ

መዝፈን ህይወቴ ነው፡፡ እስከዛሬም ህይወቴ ነበር፡፡ ወደፊትም ህይወቴ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ሴሊያ ክሩዝ
የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነው መዝፈን የጀመርኩት፡፡ በአካባቢያችን ስትራትፎርድ አይዶል በተባለ የዘፈን ውድድር ውስጥ ገባሁ፡፡ ሌሎቹ ተወዳዳሪዎች የአዘፋፈን ትምህርትና የድምጽ ስልጠና ይወስዱ ነበር፡፡ በወቅቱ እምብዛም ከቁምነገር ስላልቆጠርኩት ቤት አካባቢ ብቻ ነበር የምዘፍነው፡፡ ገና 12 ዓመቴ ነበር፤ እናም ሁለተኛ ወጣሁ፡፡
ጀስቲን ቢበር
የሻማ መደብሩ ሲቃጠል ትዝ ይለኛል፡፡
ሁሉም ዙሪያውን ቆሞ “መልካም ልደት” የሚለውን መዝሙር ሲዘምር ነበር፡፡
ስቲቨን ራይት
ከመዝፈን የሚሻል ብቸኛ ነገር የበለጠ መዝፈን ነው፡፡
ኢላ ፊትዝገራልድ
በዓለም ላይ ትልቁ መግባቢያ ሙዚቃ ነው፡፡ ሰዎች የምታቀነቅንበትን ቋንቋ ባይረዱት እንኳን ሸጋ ሙዚቃን ሲሰሙ ያውቁታል፡፡
ሌዩ ራውልስ
ፀሐይ ስትጠልቅ ከተመለከትክ፣ አንድ ትርጉም ሊኖረው ይገባል? አዕዋፍ ሲዘምሩ ከሰማህ፣ መልዕክት ማስተላለፍ አለበት?
ሮበርት ዊልሰን
ዘፈን ሁልጊዜም እጅግ ትክክለኛው ሃሳብን የመግለጫ መንገድ ነው፡፡ በጣም ግብታዊ ነው፡፡ ከዘፈን ቀጥሎ ደሞ ቫዮሊን ይመስለኛል፡፡ እኔ መዝፈን ስለማልችል ሸራዬ ላይ እስላለሁ፡፡
ጆርጂያ ኦ’ኪፌ
በዝናብ ውስጥ እየዘፈንኩ ነው፤ ዝም ብዬ በዝናብ ውስጥ እየዘፈንኩ፡፡ እንዴት ደስ የሚል ስሜት ነው! አሁንም እንደገና ደስተኛ ነኝ፡፡
አርተር ፍሪድ  

Published in ጥበብ