የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እስር ያሳስበኛል ብሏል
በኢትዮጵያ ሃሳባቸውን በነፃ የመግለፅ መብታቸውን በመጠቀማቸው ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች ከእስር እንዲፈቱ ሰሞኑን የአሜሪካ መንግስት ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የተፈረደበት የሶስት ዓመት እስር በእጅጉ ያሳስበኛል አለ፡፡
የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ሃሳብን በነፃ የመግለፅና የፕሬስ ነፃነት የዲሞክራሲ አንኳር እሴቶች መሆናቸውን በመጠቆም፤ ዲሞክራሲያዊ ነኝ የሚል መንግስት ይህን መብት የማስከበር ኃላፊነት አለበት ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገትና አፍሪካ ውስጥ ግጭቶችን ለመፍታት የምታካሂደው ጥረት በአርአያነት እንደሚጠቀስ መግለጫው አውስቶ፤ ይህንንም በመስከረም ወር ፕሬዚዳንት ኦባማ ከጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተወያዩበት ወቅት በይፋ መናገራቸውን አስታውሷል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የታሰሩ ጋዜጠኞችን በመፍታት፣ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብትንና የፕሬስ ነፃነትን የሚያስከብር አርአያነት እንዲያሳይ የአሜሪካ መንግስት ጠይቋል፡፡
የ “ፋክት” መፅሄት አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ የ “ፍትህ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረ ጊዜ በተለያዩ ህትመቶችና ባወጣቸው ፅሁፎች “ህዝብን ለአመፅ አነሳስተሃል፤ ሃሰተኛ ወሬዎችን አሰራጭተሃል” በሚል በርካታ ክሶች እንደቀረቡበት የሚታወስ ሲሆን፤  ሰሞኑን የ3 ዓመት እስር የ10ሺህ ብር ቅጣት ተወስኖበታል፡፡ ጋዜጠኛው በጠበቃው አማካይነት ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውቋል፡፡   
ከስድስት ወር በፊት አንድ ላይ የታሰሩ ዘጠኝ ጋዜጠኞችና የኢንተርኔት ፀሐፊዎችን ጨምሮ፤ ኢትዮጵያ በአለም ደረጃ በርካታ ጋዜጠኞችን ለእስርና ለስደት በመዳረግ ተጠቃሽ ሆናለች በማለት አለማቀፍ የሰብአዊ መብትና የፕሬስ ነፃነት ተቋማት በተደጋጋሚ መንግስትን ይኮንናሉ፡፡
በጋዜጠኛነት ሙያው የታሰረና የተሰደደ ጋዜጠኛ እንደሌለ የሚናገረው መንግስት በበኩሉ፤ ጋዜጠኞች የታሰሩት የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል በሚል እንደሆነና ጉዳያቸው በፍ/ቤት ውሳኔ እንደሚያገኝ ይገልፃል፡፡

Published in ዜና

ሁሉም ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሏል
     ከአራት ወር ገደማ በፊት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ አራት የፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በ10 ግለሰቦች ላይ የግንቦት 7 የሽብርተኛ ቡድን አባል በመሆን የተለያዩ ተልዕኮዎችን ተቀብለው መንግስትን በሃይል ለመጣልና የማህበራዊ ተቋማትን ለማውደም ተንቀሳቅሰዋል በሚል በትናንትናው እለት ክስ ተመሰረተባቸው፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሠረተባቸው 1ኛ ተከሳሽ በዩኒቨርስቲ የማስተርስ ተማሪ የሆነው አቶ ዘላለም ወርቅ አገኘውን ጨምሮ፣ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሃብታሙ አያሌው፣ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አብርሃ ደስታ፣ የሠማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ የሸዋስ አሠፋ እንዲሁም በግል ስራ የሚተዳደሩት ዮናታን ወልዴ፣ አብርሃም ሰለሞን፣ ሠለሞን ግርማ፣ ባህሩ ደጉ እና ተስፋዬ ተፈሪ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በአጠቃላይ በተከሳሾቹ ላይ 4 ክሶች የቀረቡ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ፤ በመንግስት “አሸባሪ” የተባለው ግንቦት 7 ቡድን ያቀረበለትን የአባልነት ጥሪ ተቀብሎ አባል በመሆን፣ ሰዎችን ለቡድኑ በመመልመል፣ ወደ ኤርትራ ሄደው እንዲሠለጥኑ በማድረግ፣ ለአመጽ ምቹ ቦታዎችን ለይቶ በመምረጥ መንግስትና ህገመንግስታዊ ስርአቱን እንዲሁም ማህበራዊ ተቋማትን በሽብር ለማፈራረስ ተንቀሳቅሷል የሚል ክስ ተመስርቶበታል፡፡  በሁለተኛ ተከሳሽነት የተጠቀሱት አራቱ የፓርቲ አባላት ህጋዊ ፓርቲን እንደሽፋን በመጠቀም የግንቦት 7 ጥሪን በመቀበል፣ አላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል፤ ከግንቦት 7 አመራር አባላት ጋርም በመገናኘት የተለያዩ የሽብር ተልዕኮዎች ተቀብለዋል የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ አቶ ዘላለምን ጨምሮ አራቱ የፓርቲ አባላት ከግንቦት 7 የሽብር ቡድን ጋር በመገናኘት ሽብር በማሴር፣ በማቀድና ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸውን ከአቃቤ ህግ ክስ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሌሎች በመዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች፣ የሽብር ቡድኑ አባል በመሆንና በሽብርተኛ ድርጅቱ ውስጥ በማናቸውም መልኩ በመሳተፍ አላማውን ለማስፈፀም ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በአቃቤ ህግ የቀረበውን ክስ በንባብ ያሰማው ችሎቱ፤ ተከሳሾቹ የሚያቀርቡትን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ብይን ለመስጠት መዝገቡን ለጥቅም 26 ቀን 2007 ዓ.ም ጠዋት ቀጥሯል፡፡

Published in ዜና

        በኢትዮጵያ ከ104 ሺ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ይገኛሉ
         የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር ቢሮ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፣ በየዕለቱ ከ200 በላይ ኤርትራውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ መግለጹን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
በኤርትራ መንግስት አስተዳደር የተማረሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ያስታወሰው የተመድ ሪፖርት፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን አደገኛ ድንበር እያቋረጡ በህገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ካለፈው መስከረም ወር አንስቶ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው ብሏል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ3ሺህ 500 በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የገለጸው የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር ቢሮ ሪፖርት፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር ከ104 ሺህ በላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
የስደተኞችን ቁጥር እንዲጨምር ያደረገው ምክንያት በሪፖርቱ እንዳልተገለጸ የጠቆመው ዘገባው፤ይሄም ሆኖ ግን አንዳንድ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ኤርትራውያን በአገሪቱ መንግስት የሚደርስባቸው ጭቆና እየከፋ መምጣቱ ለስደቱ መባባስ በምክንያትነት እንደሚያስቀምጡት ገልጧል፡፡

Published in ዜና

ቦርዱ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብሏል
ቅሬታ አቅራቢዎቹን የፓርቲው መዋቅር አያውቃቸውም ተብሏል

           የኢ/ር ግዛቸው ሽፈራውን ከስልጣን መልቀቅና ጠቅላላ ጉባኤው ሳይወስን አዲስ ፕሬዚዳንት መመረጡን የተቃወሙ የአንድነት ፓርቲ የተለያዩ ዞኖች አመራሮች የተቃውሞ ደብዳቤያቸውን ለምርጫ ቦርድ ያስገቡ ሲሆን ቦርዱ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብሏል፡፡ የፓርቲው አመራሮች በበኩላቸው፤ የተሰራ ስህተት የለም ሲሉ ከትናንት በስቲያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የኢ/ር ግዛቸው ከስልጣን መልቀቅ ተገቢ አይደለም፣ በግፊትና በጫና ነው የለቀቁት ሲሉ ሰሞኑን በራስ ሆቴል መግለጫ የሰጡት ከአፋር፣ ከባሌ፣ ከአሩሲና ሌሎች አካባቢዎች የፓርቲው ተጠሪዎች ነን ያሉ ግለሰቦች ሲሆኑ የፓርቲው አመራሮች በበኩላቸው፤ ግለሰቦቹን የአንድነት መዋቅር አያውቃቸውም ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ መጀመሪያውኑ ካቢኔያቸውን አፍርሰው ወደ ብሔራዊ ምክር ቤቱ መምጣታቸውን ያስታወሱት አመራሮቹ፤ ፓርቲው ያለ አመራር አንድም ቀን ማደር ስለሌለበት ብሄራዊ ምክር ቤቱ ባለው ስልጣን፣ የፓርቲውን ደንብ መሰረት በማድረግ ምርጫውን አከናውኗል ብለዋል፡፡
ከቀድሞው ፕሬዚዳንት የካቢኔ አባላት አንዱ የነበሩት የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን ስለጉዳዩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢ/ር ግዛቸው ስልጣን መልቀቃቸውን ይፋ ከማድረጋቸው አንድ ቀን በፊት ሁሉንም የካቢኔ አባላት ሰብስበው ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸውን በመግለጽ፣  የካቢኔ አባላቱንም መበተናቸውን በይፋ ተናግረዋል ብለዋል፡፡
በወቅቱ አመራሩን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይያዙ ተብሎ እንደነበረ የጠቆሙት አቶ ዘካሪያስ፤ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ መቀጠል አልችልም በማለታቸውና ደንቡም ስለማይፈቅድ በቀጥታ ካቢኔውን ማፍረስ አማራጭ የሌለው ሆኗል ብለዋል።
“የጠቅላላ ጉባኤው ውክልና ብሄራዊ ምክር ቤቱ አለው” ያሉት አዲሱ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ በላይ ፍቃዱ፤ “ኢ/ር ግዛቸው ካቢኔውን በትነው መልቀቃቸውን በማሳወቃቸው፣ ፓርቲውን አመራር አልባ ላለማድረግ በአስቸኳይ አመራሩ ተመርጦ ካቢኔው ሊዋቀር ችሏል ብለዋል፡፡
 የህግ ጥሰት ተፈፅሟል ያሉት ሰዎች የፓርቲው ተጠሪዎች ነን ቢሉም ከሁለቱ በስተቀር የፓርቲው የአመራር መዋቅር አያውቃቸውም  ተብሏል፡፡ በአንድነት ፓርቲ ዙሪያ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና በሰጡት ምላሽ፤ ከሁለቱም ወገኖች በቀረቡ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቦርዱ ነገሩን በትኩረት እየመረመረ ነው ብለዋል፡፡  በሌላ በኩል፤“በፖለቲከኛ እስረኞች ላይ እየተፈፀመ ያለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል” በሚል አንድነት በሰጠው መግለጫ፤ በእስር ላይ በሚገኙት የፓርቲው አመራሮች፣አቶ ሃብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየተፈፀመ ነው ብሏል፡፡
አቶ ሃብታሙ ለእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች እየደረሰበት ያለውን በደል አቤት ቢልም ቀና ምላሽ አልተሰጠውም ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ አቶ ዳንኤል ሺበሺም የታፈነ ክፍል ውስጥ እንዲቀመጥ በመደረጉ በተደጋጋሚ ለተቅማጥና ለተለያዩ በሽታዎች መዳረጉንና ወደ መጸዳጃ ቤት እንዳይሄድ መከልከሉን  ለፍ/ቤት ቢያመለክትም ምንም ምላሽ አልተሰጠውም ብለዋል፡፡

Published in ዜና
  • በ“ክልሉ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ 5ሺህ ያህል ሰዎች ታስረዋል”
  • የእንግሊዝ ጋዜጦች ኢትዮጵያ በየአመቱ የሚሰጣትን ከ9 ቢ. ብር በላይ እርዳታ ተቃውመውታል
  • የኢትዮጵያ መንግስት የእነአምነስቲን ሪፖርት መሰረተ ቢስ ነው ይላል

        በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሶስት አመታት 5ሺህ ያህል ሰዎች ኦነግን ትደግፋላችሁ፣ መንግስትን ትቃወማላችሁ በሚል ጥርጣሬ  ክስ ሳይመሰረትባቸው እንደታሰሩና በርካቶችም ለስቃይና ለሞት እንደተዳረጉ “አምነስቲ” የገለጸ ሲሆን የእንግሊዝ ጋዜጦች በየአመቱ፣ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ እርዳታ ተቃውመውታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተቋማት የሚያወጡት ሪፖርት፤ የውጭ ሃይል ጣልቃገብነትን የሚያራምድ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ይላል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚፈጽመው በደል እየከፋ መምጣቱንና ሰላማዊ ተቃውሞ ባደረጉ ዜጎች፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና በተማሪዎች እንዲሁም በክልሉ በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ እስር፣ ስቃይና ግድያ እንደሚፈጸም ገልጿል፡፡
በክልሉ በርካቶች ለእስር የተዳረጉት ሌሎች ሰዎች መንግስትን እንዲቃወሙ አነሳስታችኋል በሚል እንደሆነ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦችም ጥቃት እንደሚደርስባቸው አስታውቋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የጦር ካምፖች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ታስረው እንደሚገኙና አብዛኞቹም ከጠበቆችና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እናዳይገናኙ እንደተከለከሉ ሪፖርቱ አብራርቷል፡፡
አለማቀፋዊና ክልላዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በአፋጣኝ በጉዳዩ ጣልቃ ሊገቡና በክልሉ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ገለልተኛ የሆነ ምርመራና ማጣራት ሊደረግባቸው ይገባል ብሏል አምነስቲ፡፡
በተያያዘ ዜና የእንግሊዝ መንግስት ከፍተኛ እርዳታ ከሚሰጣቸው አገራት ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ትናንት የዘገበው ቴሌግራፍ፣ ባለፈው አመት ብቻ ከ329 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ እርዳታ መቀበሏን ጠቅሶ የጸጥታ ሃይሎች ዜጎችን ለሚያሰቃዩባት ኢትዮጵያ እርዳታ መሰጠቱን ተቃውሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በየአመቱ ከእንግሊዝ የሚያገኘውን ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ እርዳታ ለልማት ማዋል ሲገባው ዜጎችን ለመጨቆን እያዋለው ይገኛል ያለው ጋዜጣው፣ ድርጊቱን አውግዞታል፡፡ ዴይሊ ሜይልም በተመሳሳይ ሁኔታ እንግሊዝ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ ለኢትዮጵያ 1 ቢሊዮን ፓውንድ በእርዳታ መስጠቷን አስታውሶ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመንግስት ሃይሎች ለእስራት፣ ለሞትና ለስቃይ እየተዳረጉ እንደሚገኙ ማስታወቁን ገልጧል፡፡

Published in ዜና

*መጪው አገር አቀፍ ምርጫ ግንቦት 16 ይካሄዳል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮ አገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን ይፋ ያደረገ ሲሆን በተወዳዳሪ ፓርቲዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመፍታትም ቦርዱ ከምንጊዜውም በተሻለ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
ከትንት በስቲያ በሚኒስትር ማዕረግ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና እና ምክትሎቻቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤የ2007 አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ የመስጫ ቀን ግንቦት 15 እንደሆነና የመጨረሻ የምርጫ ውጤቱም ሰኔ 15  ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በምርጫ ለመወዳደር የሚችሉ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክታቸውን ከህዳር 15 እስከ ህዳር 30 የሚመርጡ ሲሆን ተወዳዳሪዎች የድጋፍ ፊርማ የሚያሰባስቡት ከታህሳስ 6 እስከ ታህሳስ 25 ይሆናል፡፡
በምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና በግል ለመወዳደር የድጋፍ ፊርማ ያሰባሰቡ እጩዎች፣ በምርጫ ክልል ፅ/ቤትና የምርጫ ጣቢያ ለይተው የመደቧቸውን ወኪሎቻቸውን ለምርጫ ክልል ፅ/ቤት የሚያሳውቁት ከታህሳስ 5 እስከ ግንቦት 5 እንደሆነ የቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ ያመለከተ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ከታህሳስ 16 እስከ ጥር 27  ይከናወናል ተብሏል፡፡
የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው ከጥር 1 ቀን እስከ የካቲት 12 ሲሆነ የተወዳዳሪ እጩዎች ማንነት ለህዝብ ይፋ የሚደረገው የካቲት 1 ቀን እንደሆነ ታውቋል፡፡ እጩዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን የካቲት 7 ጀምረው ግንቦት 13 ከምሽቱ 12 ሰዓት ያጠናቅቃሉ ተብሏል፡፡ የድምፅ መስጫ እለት ግንቦት 16፣  በጊዜያዊነት ውጤቱ ይፋ የሚደረገው ግንቦት 23፣ አጠቃላይ የምርጫ ውጤት የሚነገረው ደግሞ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም እንደሆነ  የቦርዱ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
ለምርጫው አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶች በአብዛኛው ተጠናቀዋል ያሉት የቦርዱ ኃላፊዎች፤ ያለፉትን አራት ምርጫዎች ተመክሮ ያገናዘበ የምርጫ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ከፓርቲዎች የሚቀርቡ ማናቸውንም ቅሬታዎች እየተቀበሉ መሆኑን የገለፁት ፕ/ር መርጋ፤ የቢሮ፣ የመሰብሰቢያና ሌሎች  ችግሮችን ጨምሮ የተለያዩ ቅሬታዎች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
75 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመዝግበው እውቅና ማግኘታቸውን የጠቆሙት ሰብሳቢው፤ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም ፓርቲዎች ማወያየት እንችላለን ብለዋል፡፡

Published in ዜና

 መላውን ዓለም ስጋት ላይ በጣለው የኢቦላ በሽታ የተጠቁ ወገኖችን ለመታደግ ወደ ምእራብ አፍሪካ አገራት ለመሄድ የሚፈልጉ 220 በጎ ፈቃደኞች እንደተመዘገቡ ተገለጸ፡፡ በጎ ፈቃደኞቹ በመጪው ሳምንት ልዩ ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ወደ ላይቤሪያ፣ ጊኒና ሴራሊዮን ይሄዳሉ ተብሏል፡፡
በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው በመተላለፍ በበሽታው ከተያዙት ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ ያህሉን  በአጭር ጊዜ ለሞት የሚዳርገው ኢቦላ፣ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የሚደረገው ቁጥጥር እንደቀጠለ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ በአገሪቱ በበሽታው የተያዘ ሰው አለመገኘቱን በአገር አቀፍ የኢቦላ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር የኮሚኒኬሽንና አድቮኬሲ ንዑስ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አቤል የሻነው ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል የሚገቡ መንገደኞችን የጤና ሁኔታ ለመመርመር የሚያስችሉ እያንዳንዳቸው 39ሺ ዶላር (780 ሺ ብር ገደማ)  ወጪ የሆኑባቸው ቴርሞ ለክሪን ካሜራ የተባሉ ሁለት መሳሪያዎች በጥቅም ላይ መዋላቸውን የገለፁት አቶ አቤል፤ መሳሪያዎቹ በሰዓት 1ሺህ ያህል መንገደኞችን የመመርመር አቅም አላቸው ብለዋል፡፡ አንድ ሰው በቫይረሱ በተጠቃ በ21 ቀናት ውስጥ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራል ያሉት አቶ አቤል፤ በተለይ ከምዕራብ አፍሪካ አገራት በሚገቡ እንግዶች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሽታው ወደ አገሪቱ እንዳይገባ ለመከላከል ከ3 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችን ያሳትፋል የተባለው ስልጠና በግሎባል ሆቴል እየተሰጠ ሲሆን በየዕለቱም 300 የሚደርሱ ባለሙያዎች ስልጠናውን እንደሚወስዱ ታውቋል፡፡ በሽታው ወደ አገሪቱ ከገባ በቀብር አፈፃፀም ወቅት በሚኖር ንኪኪ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመግታት ለሃይማኖት ተቋማትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ስልጠና ሊሰጥ ታቅዷል፡፡ በትላንትናው ዕለት ስልጠናው ሊሰጥ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት ለሌሎች ቀናት እንደተላለፈ ተጠቁሟል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ እስከ አሁን ድረስ 8033 ሰዎች በኢቦላ በሽታ የተያዙ ሲሆን 3865 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ 

Published in ዜና

በኦሮሚያ ክልል የሚገኙትን የአዳማና ሞጆ አካባቢዎች የሚሸፍን የዲጂታል ቶፖግራፊ ካርታ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው ጃይካ ከተባለው ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ጋር በትብብር የሚሰራው ዲጂታል ቶፖግራፊ ካርታ፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዲሱ ካርታ ኤጀንሲውን ወደ ዲጂታል የአሰራር ዘዴ እንደሚያሸጋግረው ተጠቁሟል፡፡ የአዳማና ሞጆ አካባቢዎች ለፕሮጀክቱ ስራ የተመረጡት ትላልቅ ፕሮጀክቶችና ሰፋፊ የልማት ስራዎች የሚከናወኑባቸው ስፍራዎች በመሆናቸውና ለአዲስ አበባ ከተማ ያላቸው ቅርበት ስራውን በወቅቱ ለማጠናቀቅ ይረዳል በሚል እንደሆነ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

አምቦ ጠበል የ “የኛ”ን አርማ የያዘ አምቦ ውሃ በማምረት፣በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ሊያሰራጭ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ አርማውን የያዘ ስቲከሮችን ለማሰራት ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ እንደፈጀ  ተገልጿል፡፡
ያለ ዕድሜ ጋብቻና እርግዝና፣ የፆታ ጥቃትና መሰል ችግሮች ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚሰራው “የኛ” ፕሮግራም፤ አራተኛ ምዕራፉን በነገው እለት እንደሚጀምር በይፋ ባስታወቀበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የአምቦ ውሃ ተወካይ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ሃላፊነት ለመወጣትና በ“የኛ” ፕሮግራም እየተከናወነ ያለውን ስራ ለማገዝ፣ ስምምነት መፈራረማቸውን ጠቁመው ይህንን አይነቱን የትብብር ሥራ ሲሰሩም ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የ “የኛ” ዳይሬክተር ወ/ሮ አይዳ አሸናፊ በበኩላቸው፤ “በፕሮግራሙ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ለማሳካት ከኢትዮጵያዊውና ከባህላችን ከተወለደው አምቦ ጠበል ጋር መተባበሩ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ ከድርጅቱ ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራርመናል፡፡” ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባና በአማራ ክልል  ይሰራጫል ተብለው የታሰቡት 5 ሚሊዮን ጠርሙስ የአምቦ ውሃ ምርቶች፣ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ተሰራጭተው እንደሚጠናቀቁ ተገልጿል፡፡ 

Published in ዜና

እስከ 16 አመት የሚደርስ እስር ሊፈረድበት ይችላል

የ21 አመቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወጣት ሮቤል ፊሊጶስ፤ የአሜሪካ ፖሊስ ባለፈው ሚያዝያ ወር በቦስተን ማራቶን ውድድር ላይ በተከሰተው የቦንብ ጥቃት ዙሪያ በሚያደርገው ምርመራ ሃሰተኛ መረጃ ሰጥቷል፤ ምርመራውን ሆን ብሎ አስተጓጉሏል በሚሉ ሁለት ክሶች ባለፈው ማክሰኞ በቦስተን ፌደራል ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ መባሉ ተዘገበ።
ፍንዳታው ከደረሰ ከሶስት ቀናት በኋላ፣ የቦንብ ጥቃቱ ፈጻሚ ነው ተብሎ በሚጠረጠረው ዞካር ሳርኔይ የተባለ ግለሰብ ክፍል ውስጥ የነበሩ ማስረጃዎችን አሽሽተዋል ከተባሉ ሶስት ሰዎች ጋር እንደነበር የተጠረጠረውና የግለሰቡ ጓደኛ የሆነው ወጣት ሮቤል ፊሊጶስ፣ በመጭው ጥር ወር መጨረሻ በቀረቡበት ክሶች በእያንዳንዳቸው እስከ ስምንት አመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ሮቤል በወቅቱ አደንዛዥ ዕጽ ተጠቅሞ ስለነበር፣ በክፍሉ ውስጥ ስለተፈጠረው ነገር ማስታወስ ባለመቻሉ እንጂ ሆን ብሎ አልዋሸም ያሉት የሮቤል ጠበቆች፣ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡
ሶስት ሰዎችን ለሞት፣ ከ260 በላይ ሰዎችንም ለመቁሰል አደጋ የዳረገውን የቦንብ ጥቃት ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረው ዞካር ሳርኔይ፣ በመጪው ጥር ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ የጠቆመው ዘገባው፤ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ ሞት የሚደርስ  ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ታውቋል፡፡

Published in ዜና