የዓመቱ “Top 10” ቀሽም ፖለቲከኞች  ይፋ ተደርገዋል   
በም/ቤት ስብሰባ የወሲብ ፊልም ሲመለከቱ የተያዙ ተባረሩ  
የቀድሞ የጣልያን ጠ/ሚኒስትር በታክስ ማጭበርበር ተከስሰዋል
የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት “የጐሰኝነት ፖለቲካ” ድህነትን አስፋፍቷል

ክላሺንኮቭ (AK-47) የተባለውን ለሁሉም ሥፍራ ተስማሚና ለአጠቃቀም ምቹ የሆነ  የጦር መሣሪያ በመፈልሰፍ፣ ለመላው ዓለም “እነሆ በረከት” ያሉት ሩሲያዊው “ጀግና” ሚካሄል ክላሺንኮቭ፤ ባለፈው ሰኞ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ስሰማ ማዘኔ አልቀረም፡፡ (የአፍሪካ መሪዎችና አማፅያን ባለውለታ መሆናቸውን እንዳትረሱት!) በነገራችሁ ላይ ሰውየው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልብ ችግር ሲሰቃዩ የቆዩ ሲሆን ለአንድ ወር ያህል በሆስፒታል ተኝተው የህክምና ክትትል ቢደረግላቸውም ከመሞት አልዳኑም፡፡ እሳቸውስ የእድሜ ባለፀጋ ናቸው - በ94 ዓመታቸው ነው የሞቱት፡፡ እሳቸው በሰሩት ክላሺንኮቭ ሲጠዛጠዙ በለጋ እድሜያቸው የተቀጩ አፍሪካውያንን ራሷ አፍሪካ ትቁጥረው!!  ሚኻኤል ክላሺንኮቭ በለጋ እድሜያቸው የእርሻ መሣሪያ የመሥራት ህልም ነበራቸው፡፡ (ህልሙ ነፍስ ሳይዘራ ቀረ እንጂ!) የማታ ማታም በዝነኛው ክላሺንኮቫቸው በዓለም ላይ እህል ሳይሆን ምስቅልቅል ቀውስ ዘሩበት፡፡ በህይወት ሳሉ የጦር መሣሪያ በመስራት ለህዝቦች ደም መፋሰስ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ሰላም ይነሳቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ የተጠየቁት ሚኻኤል ክላሺንኮቭ “እኔ እንቅልፌን ስለጥጥ ነው የማድረው፡፡ መስማማት አቅቷቸው የጦርነት አማራጭን የሚወስዱት ፖለቲከኞች ናቸው ተጠያቂዎቹ” በማለት ራሳቸውን ነፃ አድርገዋል (ከደሙ ንፁህ ነኝ እንደማለት!)
የAk -47  አባት የሆኑትን ሩሲያዊ ዜና ህልፈት ቀድሞ በሞባይል ቴክስት ያቀበለኝ ሁነኛ ወዳጄ፤ ሳምንቱን መላ አፍሪካ የሃዘን ማቅ ለብሳ እንደምትሰነብት ጠቆም አድርጐኝ ነበር፡፡ ለምን ቢሉ? የአህጉሪቷ ህልውና ከክላሺንኮቭ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለውና፡፡ እንዴ … ለበርካታ ዘመናት አፍሪካውያን በጦር አበጋዞቻቸው ቀስቃሽነት እርስ በእርስ የተላለቁት እኮ በእኚህ ሰው ድንቅ የፈጠራ ሥራ (“ድንቅ የፈጠራ መጥፊያ” ይሻላል!) እኮ ነው። እስቲ አስቡት … አጠቃቀሙ ቀላል ነው፣ ብርድና ሙቀት ሳይል የትም አገር ይተኩሳል፣ ዋጋውም እርካሽ ነው (ዋጋው የማይቀመሰው አሜሪካ ሰራሽ የጦር መሣሪያ ተገዝቶማ አይቻልም ነበር!) AK-47 ባይኖር እኮ አፍሪካውያን በኋላ ቀር መሳሪያ ነበር የሚተላለቁት፡፡ ሌላው ቢቀር  ከአሰቃቂው “ገጀራ” ገላግሎናል (እርስ በእርስ መተላለቁማ አዕምሮ ሳይቀር ሊቀየር አይችልም!) ይኸው በ21ኛው ክ/ዘመን እንኳን --- የአዲሲቱ አገር ደቡብ ሱዳን መሪዎች በጎሳ ተቧድነው እልቂቱን ጀምረውት የለ! (እስካሁን 1000 ሰዎች ሞተዋል!)
 የኢንካርታ መዝገበ ቃላት፤ ክላሺንኮቭ የሚለውን ቃል ሲፈታው ምን ይላል መሰላችሁ? በአሸባሪዎች ወይም በሽምቅ ተዋጊ ድርጅቶች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል በከፊል አውቶማቲክ የሆነ ሩሲያ ሰራሽ ጠብመንጃ። መዝገበ ቃላቱ እንዲህ ይፍታው እንጂ በህዝብ ምርጫ ሥልጣን ላይ እንደወጡ በድፍረት የሚናገሩ የአፍሪካ መንግስታት ሳይቀሩ በስፋት ሲጠቀሙበት የኖረ የጦር መሳሪያ ነው፡፡ Ak -47!!
እናም ሁነኛ ወዳጄ እንዳለው … ለአፍሪካ ታላቅ የሃዘን ሳምንት ነበር፡፡ ለምን ቢሉ … ድንገተኛ የሞት ዜናቸው የተሰማው ሩሲያዊ የ Ak -47 ፈጣሪ በእርግጥም የአፍሪካ ባለውለታ ነበሩና፡፡ በተለይ ለአፍሪካ መሪዎችና አማፅያን! ካላመናችሁኝ ደግሞ አፍሪካውያን ሽምጥ ተዋጊዎችንና ሥልጣን ላይ ያሉትን የአፍሪካ አምባገነን መንግስታት ልትጠይቁ ትችላላችሁ፡፡ የታሪክ ዶሴዎችም ከዚህ የተለየ ሃቅ አይነግሯችሁም፡፡ በሩሲያው “ጀግና” በተሰራው የጦር መሳሪያ ስንቶቹ ተቀናቃኞቻቸውን ዶግ አመድ አድርገው ስልጣን እንደተቆናጠጡ የየአገሩ ቤተመንግስት ይቁጠረው። እርግጥ ነው ቁጥራቸው የትየለሌ የሆኑ የአፍሪካ ንፁሃን ዜጎችም የAk -47 ሰለባ ከመሆን አላመለጡም። የሚገርመው ግን --- እስካሁን ማንም የጦር መሳሪያ ፈጣሪውን ሩሲያዊ ተጠያቂ ሲያደርግና ሲያማርር ሰምተን አናውቅም። (ባለውለታችን ናቸዋ!) የትኛውም የአፍሪካ አገር የቱንም ያህል መቶ ሺዎችና ከዚያም በላይ ህዝቦች ቢያልቁበትም መሳሪያውን ከመግዛትና ወደ አገሩ በገፍ ከማስገባት የታቀበበት ጊዜ የለም፡፡ (አፍሪካዊ መንግስት ክላሺንኮቭ ሳይንተራስ እንቅልፍ አይወስደውም እኮ!) እናም ---- በዚህ ሳምንት በሞት የተለዩት ሩሲያዊው ሜ.ቲ ክላሺንኮቭ ከማንኛውም የዓለም ክፍል ይልቅ የአፍሪካ ታላቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ (ለአፍሪካ ክላሺንኮቭ ኦክሲጂን ማለት እኮ ነው!) እንደውም ሰውየው ባለውለታ የሚለው ቃል ሳያንሳቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ እናላችሁ ---- “አፍሪካ ሌላ ታላቅ ልጇን በሞት ተነጠቀች” ብንል አላጋነንም (“መወለድ ቋንቋ ነው” አሉ!) ከሁለት ሳምንት በፊት የፍቅርና የመቻቻል ተምሳሌት የነበረውን ታላቅ ልጇን ማንዴላን ያጣችው አፍሪካ፤ ይኸው አሁን ደግሞ ለህዝቦቿ እልቂት Ak -47ን ሰርተው ያበረከቱትን ታላቅ ባለውለታ ተነጠቀች፡፡ ዛሬ እንግዲህ የፈረንጆቹ ዓመት ማጠቃለያ ላይ ስለምንገኝ የፖለቲካ ወጋችን ዓለም አቀፍ ፖለቲካ ላይ ያነጣጥራል (ግሎባላይዜሽን እኮ ነው ዘመኑ!) እናም Toptens world.com የተሰኘ ድረ ገጽ፤ የዓመቱ Top 10 “የለየላቸው ቀሽም ፖለቲከኞች” በሚል ያወጣውን መረጃ እየቃኘን ዝነኛ ፖለቲከኞችን እንታዘባለን፡፡ ድረገፁ በመግቢያው ላይ እንደሚለው፤ በመላው ዓለም ከሚገኙ ፖለቲከኞች 10 የለየላቸውን ቀሽሞች ብቻ መምረጥ አስቸጋሪና ፈታኝ ነው፤ ምክንያቱም የዓለም ፖለቲከኞች ሁሉ ምድባቸው ከዚህ ውጭ አይደለም፡፡ የማታ ማታ ግን ከብዙ ጥናትና ምርምር በኋላ እንደምንም ቅሽምናው የከፋባቸውን ወይም የበረታባቸውን 10 ፖለቲከኞች መርጠናል - ይላል ድረገፁ፡፡
“አብዛኞቹ ፈሪዎችና አጭበርባሪዎች፤ አንዳንዶቹ ስግብግቦችና ዋሾዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ አሳፋሪዎችና መሳቂያ መሳለቂያዎች ናቸው” ሲልም የዓለም ፖለቲከኞችን ዶግ አመድ ያደርጋቸዋል፡፡ (ሲያንሳቸው ነው!) እናላችሁ ----- ሁሉንም ባይሆን እንኳን የተወሰኑትን ቅሽምና የከፋባቸው ፖለቲከኞችና ለቅሽምና ያበቃቸውን ድርጊቶች አብረን እንቃኛለን (“ወዳጅህ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ” አሉ!)
የምንጀምረው የካናዳ ፖለቲከኛና የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አባል ከሆነው ሮበርት አንደርስ ነው፡፡ አንደርስ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች ላይ እንቅልፉን በመለጠጥ የሚታወቅ ፖለቲከኛ ነው(ያውም እያንኮራፈ!) ቀደም ሲል በዚሁ ክፉ ልማዱ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው አንደርስ፤ በቅርቡም እንቅልፉን ሲለጥጥ ተገኝቷል (እንቅልፎ አትሉትም!) እንቅልፉን ሲለጥጥ የነበረው የጡረተኞች ጉዳይ ኮሚቴ የሞቀ ስብሰባ ላይ ሲሆን ድንገት ከእንቅልፉ ባንኖ  ለተሰብሳቢው ድንገተኛ ሰላምታ በመስጠቱ ነው የተነቃበት ተብሏል (በእንቅልፍ ልቡ ማለት ነው!) ከእንቅልፉ በደንብ ሲነቃ ታዲያ ተሰብሳቢውን በአግባቡ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ነገር ግን ከኮሚቴው ከመባረር አላዳነውም፡፡ (በእንቅልፋምነት የኛዎቹ ባይብሱ ነው!) የሆነ ሆኖ የካናዳው ፖለቲከኛ፤ በቀሽም ፖለቲከኞች (Top 10) ዝርዝር ውስጥ 10ኛ ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡
ሮድ ታም ደግሞ በሃዋይ የሆኖሉሉ ከተማ ምክር ቤት አባል ነው፡፡ ታም በተለይ የሚታወቀው “ሆዳም የምክር ቤት አባል” በሚል ቅጽል ስሙ ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ ሆዳም የተባለው? የምክር ቤቱን የወጪ ሂሳብ እና የምርጫ ዘመቻ ገንዘብ እየመዠረጠ ሆዱን ሲሞላ ስለከረመ ነው። የራሱ ሳያንስ ቤተሰቡን፣ ባልንጀሮቹን እና የምክር ቤት አባላትን እየሰበሰበ በከተማው ባሉ ምግብ ቤቶች ያበላ ነበርም ተብሏል፡፡ ሮድ ታም የማታ ማታ ክስ የተመሰረተበት ሲሆን በሦስተኛና አራተኛ ደረጃ የሌብነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል፡፡ (እንደኛ አገር ሙሰኛ ፖለቲከኞች ማለት ነው!)
በቶፕ 10 የቀሽም ፖለቲከኞች ዝርዝር ውስጥ በ8ኛ ደረጃ የተቀመጡት አፍሪካዊ ፖለቲከኛ ናቸው - የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ኧርነስት ባይ ኮሮማ፡፡ ከ2007 እ.ኤ.አ ጀምሮ ሴራሊዮንን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ የሚገኙት ኮሮማ፤ የቀሽም ፖለቲከኞች ዝርዝር ውስጥ የገቡት በጐሰኝነት አቀንቃኝነታቸው ነው፡፡ ይሄ ጐሰኝነታቸውም በሚያስተዳድሯት አገር ውስጥ ድህነትን አስፋፍቷል በሚል የሰላ ትችት ይሰነዘርባቸዋል፡፡ (ይሄ እንኳን ከኛ የተረፈ ነው!) ፕሬዚዳንቱ ከአገራቸው ሙስናን በቅጡ ለማጥፋት ተስኗቸዋል የሚለው መረጃው፤ የጐሳቸውን አባላት የሙስና ተግባራት ማጋለጥ ወይም ለህግ ማቅረብ አልቻሉም ይላል (የጐሳቸው ባህል አይፈቅድማ!) በዚህ የተነሳም መንግስታቸው ከመልካም አስተዳደር ጋር ተፋቷል ተብሏል። (መልካም አስተዳደርና ጐሰኝነት ውሃና ዘይት ናቸው!) ሲሲ ፓቲል ደግሞ የህንድ ፖለቲከኛ ናቸው። በደቡብ ህንድ የምትገኘው የካራታንካ ግዛት ህግ አውጭ ም/ቤት አባል የሆኑት ፓቲል፤ ቀደም ሲል የሴቶችና ህፃናት ልማት ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም የካራናታካ ግዛት የህግ አውጭ ም/ቤት ስብሰባ ላይ ከእሳቸው የማይጠበቅ ወራዳ ተግባር ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡ ይሄን ወራዳ ተግባራቸውን ያጋለጡት ደግሞ ስብሰባውን ለመዘገብ በም/ቤቱ የተገኙ የቴሌቪዥን የካሜራ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ም/ቤቱ በተጋጋለ ስብሰባ ላይ ሳለ ፓቲል በሞባይል ስልካቸው የወሲብ ፊልም (pornography) ሲኮመኩሙ በጋዜጠኞቹ የካሜራ ወጥመድ ውስጥ ገብተዋል ነው የተባለው፡፡ (የወከሉት ህዝብ እንዴት ያፍርባቸው!) ማፈር ብቻ አይደለም ብግን ብሎባቸዋል እንጂ! አንዳንዶች “እንዴት ይሄን የሚያመዛዝን አዕምሮ የላቸውም?” ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ “የምክር ቤቱን ቅድስና አጉድፈዋል” በማለት የውግዘት ናዳ አውርደውባቸዋል፡፡ በውግዘት ብቻ ግን አላበቃም። ፓርቲያቸው ባደረገባቸው ግፊት ከም/ቤቱ ወጥተዋል፡፡ እኚህ ቅሌታም “ፖለቲከኛ” በቀሽም ፖለቲከኞች ዝርዝር ውስጥ በ6ኛነት ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ወደ አውሮፓ ደግሞ እንሻገር፡፡ ጣልያንን ለሦስት ጊዜ (ከ1994-2011 ዓ.ም) በጠ/ሚኒስትርነት የመሩት ሲልቪዮ በርሉስኮኒ በቀሽም ፖለቲከኞች ዝርዝር የ2ኛነት ደረጃ ተሰጥቶአቸዋል፡፡  የቴሌቪዥን ቻናልን ጨምሮ ግዙፍ የሚዲያ ኩባንያ እንዳላቸው የሚነርላቸው በርሉስኮኒ፤ የጣልያን የእግር ኳስ ክለብ (ኤ.ሲ ሚላን) ባለቤትም ናቸው፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በርሉስኮኒ፤ በቅርቡ ታክስ በማጭበርበር ወንጀል ተከሰው የአንድ ዓመት እስር የተበየነባቸው ሲሆን ብይኑ ገና ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ለአቅመ ሄዋን ካልደረሰች ሴተኛ አዳሪ ጋር በክፍያ ወሲብ ፈፅመዋል በሚል ወንጀል ተከሰውም ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ በእርግጥ ታክስ ማጭበርበር ለሳቸው “ብርቅ” አይደለም፡፡ ሦስት ጊዜ ታክስ ባለመክፈል ክስ ተመስርቶባቸው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ እኚህ የለየላቸው ቀሽም ፖለቲከኛ፤ በአንድ ወቅት የG8 አገራት እምብርት የነበረችውን አገራቸውን ጣሊያንን፤ የ2 ትሪሊዮን ዩሮ ገደማ ዕዳ ውስጥ ከተዋታል ተብሏል፡፡ (የፖለቲከኛ ቅሽምና ለአገርም ይተርፋል!)
በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ፍራንሶይስ ሆላንዴ፤ ከ1997 እስከ 2008 ዓ.ም  የፈረንሳይ ሶሻሊስት ፓርቲ አንደኛ ፀሐፊ ነበሩ። በቅርቡ በተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት መሰረት፤ ለፍራንሶይስ ሆላንዴ ፕሬዚዳንትነት ቀና አመለካከት ያለው ከጠቅላላው ህዝብ መካከል  15 በመቶው ብቻ ነው ተብሏል፡፡ በእርግጥም ደግሞ ህዝቡ አይፈረድበትም፡፡ ለምን መሰላችሁ? በእሳቸው የአመራር ዘመን ሥራ አጥነት በከፍተኛ መጠን አሻቅቧል። በታክስ ህግ ላይ ያደረጉትን ለውጥ ተከትሎም በርካታ የፈረንሳይ ባለሀብቶች አገራቸውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል (ድሮስ ሶሻሊስት!) የአውሮፓ አህጉር ፈጠራ፣ አነስተኛ የመንግስት ባጀትና የተመጠነ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም የንግድ ሥራ ፈጠራና እድገት በምትፈልግበት በአሁኑ ሰዓት፤ ከአህጉሪቱ ቀንደኛ የሶሻሊዝም አቀንቃኞች አንዱ መሆናቸውም የፈረንሳዩን ፕሬዚዳንት ለትችትና ለወቀሳ ዳርጓቸዋል፡፡ በ2013 የቀሽም ፖለቲከኞች (Top 10 worst politician) ዝርዝር ውስጥ የአንደኝነት ደረጃ ይዘዋል - የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት፡፡
እንግዲህ እኔም--- በነሐሴ ወር መጨረሻ አካባቢ ደህና ስፖንሰር ካገኘሁ የአገራችንን ቶፕ 10 ቀሽም ፖለቲከኞች ዝርዝር የማውጣት ራዕይ አለኝ። ብቻ ይቅናህ በሉኝ! (ደህና ስፖንሰር ለሚያመጣ ደህና ኮሚሽን ይከፈለዋል!)

           መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገው ሲፒጄ የተሠኘው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ጋዜጠኞችን በማሠርና በማንገላታት ኢትዮጵያ ከአለም ሁለተኛ ናት ማለቱን መንግስት እና በሃገሪቱ የሚገኙ የጋዜጠኞች ማህበራት አምርረው ሲያወግዙ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው፤ በእርግጥም ሃገሪቱ ጋዜጠኞችን እያሠረች ነው፤ ደረጃው ይገባታል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጋዜጠኞች ህብረት ፕሬዚዳንት አቶ አንተነህ አብርሃም፤ “ሲፒጄ የሃገራችንን ስም ለማጥፋት ስለሚፈልግ ነው እንጂ፣ በፃፈው ፅሁፍ የታሠረ አንድም ጋዜጠኛ የለም፡፡ 3 ጋዜጠኞች የታሠሩት አሸባሪ ተብለው ነው” ብለዋል፡፡ በማህበራችን ጥረት በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች እስር ቆሟል ሲሉም ተናግረዋል አቶ አንተነህ። የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ) ሊቀመንበር አቶ ወንደሰን መኮንን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሙያው ጋር በተያያዘ የታሠረ ጋዜጠኛ እንደሌለ ገልፀው፣ የታሠሩ ጋዜጠኞች ጉዳያቸው ሌላ ቢሆንም መፈታት አለባቸው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

የሲፒጄን መግለጫ እንደማይቀበሉትና ድርጅቱ የራሱ ተልዕኮ እንዳለው አቶ ወንደሰን ጠቁመው፤ “ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሠር በአለም ሁለተኛ መሆን አትችልም፤ ሆናም አታውቅም” ብለዋል። የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው፤ “ሲፒጄ የፖለቲካ አጀንዳ ያለውና መንግስትን በሃይል ለመለወጥ ከሚንቀሣቀሡ ድርጅቶች ጋር የተሰለፈ ድርጅት ስለሆነ፤ በተግባር ከጋዜጠኝነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም” ብለዋል፡፡ አቶ ሽመልስ፤ “እናንተ መቼ ታሠራችሁ? የማታውቁት ከማርስ የመጣና ‘የታሠረ ጋዜጠኛ አለ እንዴ?’ ሲሉም ጠይቀዋል። የሲፔጂ የአፍሪካ ወኪል፣ በ97 ምርጫ የቅንጅት አመራር የነበረና የኢትዮጵያን መንግስት በሃይል ለመገልበጥ የሞከረ ግለሠብ ያሉት አቶ ሽመልስ፤ እንዲህ ያሉግለሠቦች እየፈተፈቱ የሚያቀርቡለትን ነገር ሲፒጄ እየተቀበለ ያስተጋባል ብለዋል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና በሠጡት አስተያየት፤ መንግስት ጋዜጠኞችን እንደሚያስርና እንደሚያንገላታ ለማረጋገጥ እስር ቤት ሄዶ ማየት ይቻላል ብለዋል፡፡

የታሠረ ጋዜጠኛ የለም እየተባለ መነገሩ የተለመደ ቀልድ ነው ያሉት ዶ/ር መረራ፤ እነ እስክንድር፣ ውብሸት እና ርዕዮት በጋዜጠኝነታው እንጂ ሽጉጥ ሲሠርቁ አይደለም የታሠሩት ብለዋል፡፡ “ለመሆኑ እዚህ አገር ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገት ማህበር አለ እንዴ?” በማለት የጠየቁት ዶ/ር መረራ፤ “የነፃ ጋዜጦች እና የጋዜጠኞች ህልውና ከፖለቲካ ምህዳሩ ጋር አብሮ የተዳፈነ ነው” ብለዋል። የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ በበኩላቸው፤ ሲፔጂ መግለጫውን ሲያወጣ የራሱ መስፈርት እንዳለውና ዝም ብሎ እንደማይዘላብድ በመግለፅ፣ ሪፖርቱ ትክክለኛ መሆኑን ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ ሃሣባቸውን በነፃነት የሚገልፁ ሠዎች በአደባባይ የሚሠቃዩባት፣ ጋዜጠኞች እስር ቤት የሚታጎሩባት ማተሚያ ቤቶች መንግስትን የሚተች ጋዜጣ አናትምም የሚሉባት፣ ጋዜጦች ተዘግተው ጋዜጠኞች የተሰደዱባት አገር መሆኗን በተጨባጭ እናውቃለን” ብለዋል አቶ ዳንኤል፡፡ የታሠሩት ጋዜጠኞች ከሙያው ጋር በተያያዘ አይደለም መባሉን እንደማይቀበሉት አቶ ዳንኤል ገልጸው፤ ከነፃው ፕሬስ ጀማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው እስክንድር ነጋ፤ ለሃሣብ ነፃነት የቆመ የመብት ተከራካሪ መሆኑ መታሠብ አለበት ብለዋል፡፡

Published in ዜና

መገናኛ አካባቢ ወደ ጉርድ ሾላ በሚወስደው መስመር፣ አንድ መንገደኛ ትናንት ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ካልተሳፈርኩ ብሎ ሾፌሩን ወንደሰን ደምሴን በሽጉጥ ገደለ፡፡ “ታክሲው ውስጥ ካልተሳፈርኩ፣ አትሳፈርም” በሚል በተነሳው ጭቅጭቅ፣ ሾፌሩን ገድሏል የተባለውን ደጀኔ ገመቹ በቁጥጥር ስር እንደዋለ የገለፀው ፖሊስ፤ የአይን ምስክሮችን ቃል በመቀበል ምርመራ እያካሄደ ነው፡፡ ታክሲ እየጠበቁ የነበሩ የአይን ምስክሮች በወቅቱ አቶ ደጀኔ እጁን በማወዛወዝ ሚኒባስ ታክሲውን እንዳስቆመ ተናግረው፣ ከሾፌሩ ጋር ጭቅጭቅ እንደተፈጠረ ገልፀዋል፡፡ አቶ ደጀኔ በታክሲው ለመሳፈር ሲጠይቅ፣ ሾፌሩ “ቤተሰቤን ነው የጫንኩት፣ ሌላ ሰው አላስገባም” በማለት ምላሽ እንደሰጠው በአካባቢው የነበሩ መንገደኞች ተናግረዋል፡፡ ታክሲ የሚጠባበቁ ብዙ ሰዎች በአካባቢው ስለነበሩ፣ ጭቅጭቁን ከመነሻው እስከ መጨረሻው የተመለከቱ እማኞች በርካታ ናቸው፡፡ የፖሊስ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የሾፌሩ አባት ታክሲው ውስጥ ነበሩ፡፡ “አትሳፈርም የምትለኝ ንቀት ነው” በሚል ክርክርና “የጫንኩት ቤተሰቦቼን ስለሆነ ሌላ ሰው አልጭንም” በሚል ምላሽ በተባባሰው ጭቅጭቅ፣ አቶ ደጀኔ ሽጉጥ እንዳወጣ እማኞች ተናግረዋል፡፡ ሽጉጡን ሾፌሩ አንገት ስር በመደገን ነው የተኮሰው ብለዋል-ምስክሮች፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ዲቪዥን ክፍል ተወካይ፣ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

Published in ዜና

ፓርቲው ዛሬና ነገ አዲሱን ፕሬዚዳንት ይመርጣል

በደቡብ ክልል፣ በጋሞ ዞን በቁጫ ወረዳ፣ ከመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከ1ሺ በላይ ነዋሪዎች መታሰራቸውን “አንድነት” ፓርቲ ተቃወመ፡፡ በቁጫ ማህበረሰብ ላይ የሚደርሰው የመብት ረገጣ እንዲቆም ለማሳሰብ ሰላማዊ ሰልፍ አደርጋለሁ ብሏል፡፡ ከትላንት በስቲያ ፓርቲው በፅ/ቤቱ “የቁጫ ህዝብ ጥያቄ የሚፈታው የዜጎች መብት ሲከበር ነው” በሚል በሰጠው መግለጫ፤ በቁጫ ወረዳ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣ እየተባባሰ በመምጣቱ፣ በፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሚመራ ቡድን ወደ ሥፍራው በመላክ መረጃ ካሰባሰበ በኋላ፣ በወረዳው ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት መርምሮ ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቁሟል፡፡ በፓርቲው ብሄራዊ ኮሚቴ ፀሀፊ እና የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል በአቶ ትእግስቱ አወል የተመራው ቡድኑ፤ በቁጫ ለአራት ቀናት ባደረገው የመረጃ ማሰባሰብ ስራ 1015 ሰዎች በሰላም በር ፖሊስ ጣቢያ፣ በአርባ ምንጭና በጨንቻ ወህኒ ቤቶች እንደታሰሩ ማረጋገጡ ተገልጿል፡፡ ህዳር 14 ቀን 2006 ዓ.ም አቶ ዛራ ዛላ የተባሉ የሁለት ልጆች አባት፣ ኮዶ ኮኖ በተባለ ቀበሌ ውስጥ በጥይት ተመትተው ህይወታቸው ማለፉን የገለፁት የቡድኑ መሪ፤ አባወራው በጥይት ሲመቱ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ የስጋት ሳንታ፣ የገዢው ፓርቲ የወረዳው ድርጅት ጉዳይ ሀላፊ አቶ አሸብር ደምሴ እና የወረዳው የፀጥታ ሀላፊ አቶ አያኖ መለና በስፍራው እንደነበሩ ከአይን እማኞች መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

የወረዳው ህዝብ በአካባቢው ምንም አይነት ልማት ባለመካሄዱና በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፍ እንዲሳተፍ ዕድል ባለማግኘቱ፣ በቁጭት የማንነትና የመብት ጥያቄ ማንሳቱን የገለፁት አቶ ትዕግስቱ፤ ይሄን ተከትሎም የመብት ረገጣና የማፈናቀል ተግባር እየተባባሰ መጥቷል ብለዋል፡፡ የፓርቲው የብሄራዊ ም/ቤት አባል፣ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ኃላፊና የደቡብ ቀጠና ሀላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ በበኩላቸው፤ “የወረዳው ህዝብ ተወላጅ እንደመሆኔ የአካባቢውን ህዝብ እንግልትና የመብት ጥሰት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ” ካሉ በኋላ፤ የመብት ጥሰቱ እንዲቆም የአካባቢው ሽማግሌዎች ጠ/ሚኒስትሩን ለማነጋገር አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ሰሚ በማጣት መመለሳቸውን ተናግረዋል።

“በህዝቡ ላይ በሚደርስበት እንግልት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ መፍትሄ ለማፈላለግ እንቅስቃሴ ሳደርግ ከአካባቢው ባለስልጣናት ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶብኛል” ብለዋል-አቶ ዳንኤል፡፡ የመብቱ ጥሰቱ እንዲቆም መንግስት እርምጃ መውሰድ አለበት ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ይሄ ካልሆነ ግን ፓርቲያቸው በቁጫ ወረዳ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ማቀዱን ገልፀዋል፡፡ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሀላፊና የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስዩም መንገሻ በበኩላቸው፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት በክልል ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባም መባባሱን ጠቅሰው፤ ዛሬና ነገ ፓርቲው ለጠራው ጠቅላላ ጉባኤ አዳራሽ ለማግኘት ብርቱ ፈተና እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡

የልኡካኑ መሪ አቶ ትዕግስቱ አወልን ጨምሮ ሰባት አባላት በአካባቢው ባለስልጣናት “አፍራሽ ተልዕኮ ይዛችሁ መጥታችሁ ስለሚሆን እንጠረጥራችኋለን” ተብለው ከአራት ሰዓታት በላይ መታሰራቸውን ገልፀዋል፡፡ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ልዑካን ባቀረቡት ሰፊ ሪፖርት ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ፓርቲው ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ “በቁጫ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ረገጣ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የደረሰውን ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ ወገን እንዲቋቋምና እንዲጣራ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወስን፤ ቁሳዊ፣ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጐች የሞራል ካሳ እንዲከፈላቸው፣ የቁጫ ወረዳ ተወላጅ በሆነው የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር ላይ እየደረሰ ያለው ማሳደድና ማዋከብ በአስቸኳይ እንዲቆም” ሲል በአቋም መግለጫው የጠየቀው ፓርቲው፤ ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት ተቃውሞውን እንደሚገልፅ አስታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርቲው ዛሬና ነገ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትን፣ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርትን የሚያዳምጥ ሲሆን የውሳኔ ሃሳቦችንም እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ፓርቲው በሁለቱ ቀናት ጉባኤ አዲሱን ፕሬዚዳንት እንዲሁም የምክር ቤትና የኦዲት ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን እንደሚመርጥ የተገለፀ ሲሆን የፓርቲውን ፕሮግራምና ደንብ የማሻሻያ ረቂቆች መርምሮም እንደሚያፀድቅ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

አራት የት/ቤቱ ሰራተኞች ከስራ ታግደዋል

             የምሥራቅ ጮራ መዋለ ህፃናትና አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የመዋዕለ ህፃናት ተማሪ የነበረችው የ5 ዓመቷ ህፃን ሳባህ አማን ከት/ቤቱ 3ኛ ፎቅ ላይ ወድቃ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በህክምና ስትረዳ ቆይታ በአራተኛ ቀኗ ባለፈው እሁድ ህይወቷ አልፏል፡፡ ጉሊት በመነገድ ከሚተዳደሩ አክስቷና ከ12ኛ ክፍል ተማሪ እህቷ ጋር ትኖር የነበረችው ሕፃን በአሁኑ ዓመት ነበር ትምህርት ቤት የገባችው፡፡ ለብቻው ከተከለለው መዋዕለ ህፃናት እንዴት ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብታ፣ ከፎቅ ላይ እንደወደቀች እንደማያውቁ የተናገሩት ቤተሰቦች፤ ህፃኗን ስትወድቅ ማንም እንዳልነበረና የትምህርት ቤቱ የካፍቴሪያ ሰራተኛ መሬት ላይ ወድቃ እንዳገኛት ጠቁመዋል፡፡ ልጅቷ ስትወድቅ እንዴት አስተማሪዎች ወይም ሞግዚቶች እንዳላዩ ት/ቤቱን መጠየቃቸውን የገለፁት ቤተሰቦች፤ ከት/ቤቱ “ስብስባ ላይ ነበርን” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ የምስራቅ ጮራ ት/ቤት ርእሰ መምሕር አቶ ስንታየሁ አንሺሱ ስለ አደጋው ሲናገሩ፤ “ሳምንታዊ ስብሰባ የምናደርግበት ቀን ስለነበር አጠቃላይ የት/ቤቱ መምህራንና ሰራተኞች ተሰብስበን ሳለ ከቀኑ 9፡40 ላይ አንዲት ተማሪ ከፎቅ ወድቃለች ተባልን።

ወዲያው ህፃኗን አንስተን ወደ ምግባረ ሰናይ ሆስፒታል ወሰድናትና ወደ ጥቁር አንበሳ ላኩን። እዚያም ከፍለን አሳከምናት” ብለዋል፡፡ ሆኖም ህፃኗ በወደቀች አራተኛ ቀኗ ህይወቷ አልፏል፡፡ ህፃኗ እንዴት ትምህርት ቤት ውስጥ ለብቻዋ እንደቀረች የተጠየቁት ርዕሰ መምህሩ፤ ብቻውን እንዳልነበረችና 5 ህፃናት አብረዋት እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ህፃናቱን ለብቻቸው ትተው ስብሰባ መግባታቸው አግባብ ነው ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ ስንታየሁ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን በጊዜ እንዲወስዱ ማስታወቂያ መለጠፋቸውንና በቃልም መንገራቸውን ገልፀዋል፡፡ በህፃኗ ላይ ለደረሰው የሞት አደጋ ተጠቂው ማን እንደሆነና የተወሰደ እርምጃ ስለመኖሩ የተጠየቁት የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር፤ “ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን አራት ሰራተኞች ከስራ አግደናል፤ ሁለት ሞግዚቶችና ሁለት ጥበቃዎች ደግሞ ጉዳያቸው በዲሲፕሊን ኮሚቴ እየተጣራ ነው” ብለዋል፡፡

ት/ቤቱ ለቀብር 2500 ብር ብቻ እንደሰጣቸው የገለፁት የሟች ቤተሰብ፣ ት/ቤቱ ካሣ እንዲከፍላቸው ጠይቀዋል፡፡ የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር በበኩላቸው፤ ት/ቤቱ የመንግስት እንደሆነና ካሣ ለመክፈል ጉዳዩ በህግ መያዝ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ “እስከዚያው ግን ክፍለከተማን አናግረን፣ በየካ ክፍለ ከተማ ባሉ ት/ቤቶች እየዞርን መዋጮ ለመሰብሰብ አስበናል” ብለዋል፡፡ ይሄ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ፖሊስ የህፃኗን አሟሟት በመመመርመር ላይ እንዳለ ለማወቅ ችለናል፡፡

Published in ዜና

ለ3 ሠአታት በኢትዮጵያ ቆንስላ ላይ ተቃውሞአቸውን አሠምተዋል

            ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ከተለያዩ የሣውዲ አካባቢዎች በመሠባሠብ መጠለያ ጣቢያ የገቡ ስደተኞች፤ የኢትዮጵያ ቆንስላ ከፍተኛ እንግልት እንዳደረሰባቸው በመግለጽ ባሰሙት ተቃውሞ ከሳውዲ ፖሊስ ጋር ተጋጩ፡፡ እጃቸውን ለፖሊስ እንደሰጡና በ10 አውቶቡሶች ተጭነው ሹማሲ ወደተሠኘው የመጠለያ ጣቢያ እንደገቡ የገለፁት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከገቡበት ቀን ጀምሮ ለአምስት ቀናት በኢትዮጵያ ቆንፅላ ዳተኝነት የጉዞ ሰነድ በጊዜ ሣይዘጋጅልን ለእንግልት ተዳርገናል ብለዋል፡፡ ያለ ጉዞ ሰነድ መንገላታታቸውን በመወቃም እሁድ እለት በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ለ3 ሰዓታት ያህል ብሶታቸውን እንዳሰሙ ስደተኞቹ ተናግረዋል፡፡ የሃገሪቱ ፖሊስ አመፅ አስነስተዋል ያላቸውን ስደተኞች ለመደብደብ ሌሊት ወደ ጣቢያው እንደገባ ስደተኞቹ ጠቅሰው፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሠባቸውና በፖሊስ ጥይት የተመቱ እንዳሉም ገልፀዋል፡፡ ኤምባሲው ወደ ሃገር ቤት ትመለሣላችሁ ብሎ ባቀረበው ጥሪ ወደ መጠለያ ጣቢያው እንደገቡ የተናገረች አንዲት ስደተኛ ለኤምባሲው ሰራተኞች ብንደውልም ድብደደባው ካለቀ በኋላ ነው የደረሱት ብላለች፡፡

በድብደባው እንደተጎዳ የተናገረ ሌላው ስደተኛ በበኩሉ፤ የኤምባሲው ሰራተኞች ዘግይተው ከመድረሳቸውም በተጨማሪ እንደቆሠልን እያዩ፣ ወደ ህክምና ቦታ ለመውሠድም ሆነ እርዳታ ለማድረግ አልሞከሩም ሲል አማሯል፡፡ ከተቃውሞና ከግጭቱ በኋላ፤ ለሴቶችና ለህፃናት ቅድሚያ በመስጠት የመመለሻ ሰነድ ተዘጋጅቶ እየተሰጣቸው መሆኑን የተናገሩት ስደተኞች፤ በድብደባ የተጐዱትን ጨምሮ በርካታ ወንዶች አሁንም በመጠለያ ጣቢያው እየተንገላቱ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሣደር ዲና ሙፍቲን አነጋግረን በጉዳዩ ላይ በሠጡን ምላሽ፤ በወቅቱ በሚዲያዎች የተነገረውን ያህል ባይሆንም፣ “ወደ አውቶቢስ ግቡ አንገባም” የሚል ችግር ተፈጥሮ እንደነበር ጠቅሰው፤ አንዲት ሴት ከመጐዳቷ ውጪ በሌሎች ላይ የደረሠ ጉዳት እንደሌለ ሣውዲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንፅላ ፅ/ቤት ጠይቀው መረዳታቸውን ገልፀዋል፡፡ ከ145ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸውን ያስታወሱት አምባሣደር ዲና፤ አሁንም በመደበኛ በረራዎች በአማካይ እስከ 300 ሠው እየተመለሠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በደቡብ ሱዳን ያለውን ውዝግብ ተከትሎ በሃገሪቱ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መንግስት ከሌሎች የኢጋድ አባል አገራት ጋር በመሆን የ24 ሠአት ክትትል እያደረገ መሆኑን ቃል አቀባዩ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና
Saturday, 28 December 2013 11:10

የኢትዮ ቴሌኮም ማስተባበያ

           ጋዜጣችሁ ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 12 ቀን 2006 ዓ.ም እትሙ ላይ፣ “ከዓመት በፊት ለተበላሸ ሲሚንቶ ማስቀመጫ ከ30ሺ ብር በላይ ወርሃዊ ኪራይ ይከፈላል” በሚል ርዕስ ለቀረበው ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ የሚከተለውን ምላሽ አቅርበናል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የዜና ዘገባው ሚዛናዊነት የጎደለው ከመሆኑም ባሻገር በሃቅ ላይ ያልተመሰረተ፣ አንባቢን የሚያሳስት እና የኩባንያችንን ገጽታ የሚያጎድፍ ነው፡፡ በዜና ዘገባው መነሻ “በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ ለቴሌ ታወሮችና የኔትወርክ ግንባታ ከጅቡቲ ተገዝቶ የገባው ሲሚንቶ ከአንድ ዓመት በፊት መበላሸቱ ቢታወቅም በየወሩ ከ30ሺ ብር በላይ ለግለሰቦች ኪራይ እየተከፈለ የህዝብና መንግስት ሀብት እየባከነ እንደሚገኝ---” ሲል የፈጠራ ሃተታውን ይጀምራል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ሌሎች የሃገራችን ክልሎች ሁሉ በተለይ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማና በክልሉ ባሉ ወረዳዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እና ለሌሎች ንብረቶች ማስቀመጫ የሚያገለግል ግምጃ ቤት በከተማዋ ከሚገኝ የግል ድርጅት ተከራይቶ ሲጠቀም መቆየቱና አሁንም እየተጠቀመበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዘገባው ተቋሙ መጋዘን መከራየቱ የተገለፀው ትክክል ቢሆንም መጋዘኑ የሚያገለግለው ግን ለሲሚንቶ ማስቀመጫ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና ቁሳቁሶች ለማስቀመጥ ጭምር ነው፡፡

ምንም እንኳን በዘገባው እንደተገለፀው፣ ከንብረቶቹ መካከል የተበላሹ ሲሚንቶዎች ቢኖሩም መጋዘኑ ግን ለፕሮጀክቶች ሥራ የሚያገለግሉ የተለያዩ ንብረቶች ማኖሪያነት እና ለሌሎች ግብዓቶች ማስቀመጫነት እያገለገለ በመሆኑ፣ በዜናው እንደተጠቆመው ያለ አገልግሎት ለመጋዘኑ በከንቱ ክፍያ እየተፈፀመ እንዳልሆነ ውድ አንባቢያን እንዲረዱልን እንፈልጋለን፡፡ ሌላው የዘገባው ስህተት ደግሞ የወርሃዊ ክፍያ መጠን ላይ ነው፡፡ በዜናው እንደተጠቀሰው፣ ለመጋዘን ኪራይ የሚከፈለው ወርሃዊ ክፍያ 30ሺ ብር ሳይሆን 12,360 ብር ነው፡፡ መጋዘኑ በአሁኑ ሰዓትም በእንቅስቃሴ ላይ ለሚገኘው ለቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችና ለሪጅኑ የኦፕሬሽን ስራ የሚሆኑ ንብረቶች የሚቀመጡበትና ለነዚህ ሥራዎች አገልግሎት እየሰጠ ያለ ሆኖ ሳለ “ጥቅም ላይ ለማይውሉ ሲሚንቶዎችና ብረቶች ያለ አግባብ ኪራይ እየተከፈለ ይገኛል” በሚል መዘገቡ ስህተት ከመሆኑም በላይ የአንድ ወገን መረጃን ብቻ በዋቢነት በመጠቀም ለአንባቢያን የቀረበ በመሆኑ የዘገባውን ሚዛናዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡ በጥቅሉ ዜናው ሲዘገብ መረጃውን ከሚመለከተው አካል ማጣራትና ሚዛናዊ ማድረግ እየተቻለ፣ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ የተሳሳተ መረጃ መቅረቡ አግባብ አይደለም፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ

Published in ዜና

“ሸማመተው” በሚለው አልበሟ ከፍተኛ እውቅናን ያገኘችው ድምፃዊት ሚካያ በኃይሉ፤ በ36 አመቷ ባደረባት ህመም በህክምና ስትረዳ ቆይታ ባለፈው ማክሰኞ ሌሊት አርፋለች፡፡ ድምፃዊቷ ብዙ መሥራት ስትችል ያለ ዕድሜዋ በማረፏ ብዙ አድናቂዎቿ አዝነዋል፡፡ ለሶስት ወራት በደም ሥር መቆጣትና በከፍተኛ የጨጓራ ህመም ስትሰቃይ የቆየችው ሚካያ፤ ለህክምና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ገብታ ህይወቷ እንዳለፈ ታውቋል። በአዲስ አበባ የተወለደችው ሚካያ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ውስጥ የማስተርስ ድግሪዋን የመመረቂያ ፅሁፍ እየሰራች ነበር፡፡ በ2010 ኮራ የሙዚቃ ሽልማት ላይ ለእጩነት የደረሰችው ሚካያ፤ በባህልና ቋንቋ ላይ የሚያተኩር የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመስራት እየተንቀሳቀሰች እንደነበር ታውቋል፡፡ ድምፃዊቷ የአንዲት ሴት ልጅ እናት የነበረች ሲሆን የቀብር ስነስርዓቷ ባለፈው ረቡዕ በለቡ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡ የአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል በሚካያ በኃይሉ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቿ፣ ለወዳጆቿና ለአድናቂዎቿ መጽናናትን ይመኛል፡፡

Published in ዜና


“ዲግሪ ያላቸው በየአስተዳደሩ እንዲገቡ መደረጉ አግባብ አይደለም” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት፣ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ እያካሄደ ያለውን አዲስ የመተዳደሪያ ደንብ የማፅደቅ ሂደት እና መዋቅራዊ ለውጥ አጥብቀው እንደሚቃወሙ የሃገረ ስብከቱ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ለቅዱስ ፓትሪያርኩና ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አስታወቁ፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለፅ/ቤቶቹ ባስገቡት ደብዳቤ፤ የሃገረ ስብከቱ አዲስ መተዳደሪያ ደንብ ሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ሳይሳተፉበት በጥቂት አመራሮች ብቻ የተቀረፀና በውይይት ያልዳበረ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ ከነባሩ ህገ ቤተ ክርስቲያንና ከቃለ-አዋዲ ደንብ ጋር የሚጋጭና የሚጣረስ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “ደንቡ፤ ነባሩን የቤተክርስቲያኒቱን ሠራተኛ በማፈናቀል በምትኩ ስለቤተ ክርስቲያን ትምህርት ምንም እውቀት የሌላቸውን ግለሠቦች በስመ ድግሪና ዲፕሎማ በመሠግሠግ የቤተክርስቲያኗን ሙሉ አስተዳደራዊ መዋቅር ለመቆጣጠር ያለመ ነው” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡

አዲሱን መዋቅር ያዘጋጁት አካላት ማንነታቸው በግልፅ እንደማይታወቅ በደብዳቤያቸው የጠቀሡት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የቤተክርስቲያኗ የመጨረሻ ስልጣን ያለውን ቅዱስ ፓትርያርክ ስልጣንን በመገደብ፣ ቤተክርስቲያኗ የእነዚህ አካላት ሠለባ እንዳትሆን ስጋት አለን ብለዋል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን ቃለ አዋዲ ያልጠበቀ ነው ያሉትን አዲሱን መተዳደሪያ ደንብ እንደማይቀበሉትም አስተዳዳሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ ለቅሬታው መነሻ የሆነው ደንብ፣ ህግ በማርቀቅና በማዘጋጀት ከፍተኛ ልምድና እውቀት ባላቸው ገለልተኛ ምሁራንና የቤተክርስቲያኗ ሊቀ ሊቃውንት እንዲሰናዳ የጠየቁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ህጉን አርቅቋል የተባለውን ማንነቱ ማህበር ፓትሪያርኩ እንዲያጣሩ ተጠይቀዋል፡፡ “አዲሱ ደንብ የካህናት ቅነሣ መርሃ ግብርም እንዳካተተ በግልፅ ተረድተናል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “ድርጊቱ መንግስት ስራ አጥን ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት የሚፃረር ነው” ሲሉ ያጣላሉት ሲሆን ብዙ ሊቃውንትን ከስራ በማፈናቀል ለችግር እና ለእንግልት የሚዳረግ በመሆኑ ህጉ መፅደቅ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የፓትርያርኩ ልዩ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ታምሩ አበራ የቅሬታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤ ወደ ፅ/ቤት ሳይገባ በቀጥታ ለፓትርያሪኩ የደረሰ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ምላሽም ሆነ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸግራቸው ተናግረዋል፡፡ ቅሬታ አለን የሚሉ ወገኖች በተናጥል ከሚቀርቡ፣ ለቤተክርስቲያኗ ይጠቅማል የሚሉትን ኮሚቴ መርጠው ሃሣባቸውን በማደራጀት ቢያቀርቡ እንደሚሻል የጠቆሙት ሃላፊው፤ የእነሡ ሃሣብ ተቀባይነት ባያገኝም እንኳ በውይይት ለመተማመን ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

ታዳጊው አምበሴ አስቻለው ሰው ለመግደል በማሠብ ተበዳይን ደረቱ ላይ ስድስት ቦታዎች ላይ በጩቤ በመውጋት የቀኝ ሳምባው ላይ የደም መፍሰስ ጉዳት እንዲደርስበት በማድረጉ በፈፀመው ተራ የሆነ የሰው ግድያ ወንጀል ሙከራ መከሠሡን የአቃቢ ህግ የክስ ዝርዝር ያስረዳል፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመው ጳጉሜ 5 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 3 ሰዓት ሲሆን ቦታውም ልደታ ክ/ከተማ ቀበሌ 31 ልዩ ቦታው ቆጨ ሠፈር ነው፡፡ በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ለወንጀሉ ምክንያት የሆነው ፍሬ ሐሳብ ባይገለፅም ታዳጊው ሰው ለመግደል አስቦ የፈፀመው ነው ተብሏል፡፡ ሠሞኑን የዋለው የከፍተኛው ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 11ኛው ችሎት ተከሳሹ ከዚህ በፊት ወንጀል ፈፅሞ የማያውቅ መሆኑንና ዕድሜው 16 ዓመት መሆኑን ከግምት በማስገባት በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡ ከተፈታ በኋላም ለ2 ዓመታት ከህዝባዊ መብቱ እንዲታገድም ታዟል፡፡

Published in ዜና
Page 2 of 16