በፊፋ እና በፍራንስ ፉትቦል ትብብር ዘንድሮ ለሶስተኛ በሚዘጋጀው የዓመቱ ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋቾች፤ አሰልጣኞች እና ምርጥ ቡድን ምርጫ ላይ በየዘርፉ ለመጨረሻው ፉክክር የቀረቡት እጩዎች በየዘርፉ ከሰሞኑ ታውቀዋል፡፡ በድምፅ አሰጣጡ ሂደት የፊፋ አባል አገራት የሆኑ 209 ፌደሬሽኖች በብሄራዊ ቡድኖቻቸው ዋና አሰልጣኞች እና በአምበሎች፤ እንዲሁም ታዋቂ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሚዲያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ዓመታዊው የዓለም እግር ኳስ ክዋክብት የሽልማት ስነስርዓት ከ1 ወር በኋላ በዙሪክ የሚካሄድ ነው። በከፍተኛ ደረጃ እያከራከረ በሚገኘው የዓለም ኮከብ ተጨዋች ምርጫ ለመፎካከር የመጨረሻ እጩ ሆነው የቀረቡት ሶስት ተጨዋቾች አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ፤ ፖርቱጋላዊው ክርስትያኖ ሮናልዶ እና ፈረንሳዊው ፍራንክ ሪበሪ ናቸው፡፡ በዓለም ኮከብ አሰልጣኝ ምርጫ በመጨረሻ ተፎካካሪነት የቀረቡት ደግሞ የማንችስተር ዩናይትድ ክለብ አሰልጣኝ የነበሩት ስኮትላንዳዊው ሰር አሌክስ ፈርጉሰን፤ ባለፈው ዓመት ከባየር ሙኒክ ጋር የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስተው የተሰናበቱት ጀርመናዊው ጁፕ ሃይንከስ እና የቦርስያ ዶርትመንዱ አሰልጣኝ ጀርመናዊው የርገን ክሎፕ ናቸው፡፡

በዓመቱ ምርጥ ጎል ምርጫ ለፑሽካሽ አዋርድ በመፎካከር ደግሞ ዝላታን ኢብራሞቪች፤ ኔማንጃ ማቲች እና ፓብሎ ኔይማር ተመርጠዋል፡፡ ለ2013 የዓለም ምርጥ ቡድን የሚበቁ 11 ተጨዋቾን ለመምረጥ የዓለም አቀፉ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር አባላት የሆኑ 55ሺ ተጨዋቾች በሚሰጡት ድምፅ መሰረት የመጨረሻ እጩዎች ሆነው የቀረቡም ተለይተዋል፡፡ ለምርጥ 11 ቡድኑ የቀረቡ የመጨረሻ እጩዎች 5 ግብጠባቂዎች፤20 ተከላካዮች 15 አጥቂዎችና 15 አማካዮች ናቸው፡፡ ሊዮኔል ሜሲ ላለፉት 4 ዓመታት የወርቅ ኳሱን አከታትሎ በማሸነፍ በመጨረሻ እጩነት የቀረበ ሲሆን ዘንድሮ ካሸነፈ ለአምስተኛ ጊዜ የሚሸለምበት ይሆናል፡፡ ክርስትያኖ ሮናልዶ በበኩሉ የወርቅ ኳስ ሽልማቱን በ2008 እኤአ ላይ ብቻ ተሸልሞበታል፡፡ ክርስትያኖ ሮናልዶ የዘንድሮውን የወርቅ ኳስ ሽልማት እንደሚያሸንፍ ግምት እያገኘም ነው፡፡ ሰሞኑን ታዋቂው የስፖርትመፅሄት ዎርልድሶከር ሮናልዶን የዓመቱ የዘንድሮ ኮከብ አድርጎ ከመረጠው በኋላ የወርቅ ኳሱንም እንደሚወሰድ ያመለክታል ተብሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት በዎርልድ ሶከር መፅሄት ኮከብ ሆነው ከተመረጡት 14 ተጨዋቾች የወርቅ ኳስ ተሸላሚ ለመሆን መብቃታቸው ለዚህ ምክንያት ሆኖ ነው፡፡

ክርስትያኖ ሮናልዶ ባለው ጎል የማስቆጠር ወቅታዊ ብቃት፤ ፖርቱጋልን በመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ማጣርያ ጨዋታ በሰራው ሃትሪክ ወደ ዓለም ዋንጫ በማሳለፉ የመመረጥ እድሉ ሰፊ እንደሆነ እየተገለፀ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱት ሁለት የወርቅ ኳስ ሽልማቶች ሮናልዶ በድምፅ ብዛት ሜሲ እየበለጠው በሁለተኛ ደረጃ አጠናቅቋል፡፡ ዘንድሮ ሊያሸንፍ እንደሚችል ግምት ቢኖርም ከፊፋ ባለስልጣናት የገባው አተካታ ተፅእኖ ሊፈጥርበት ይችላል፡፡ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር በኦክስፎርድ ተማሪዎች ፊት እሱን በተመለከተ በሰጡት አስተያየትና ባህርይውን ለመግለፅ በይፋ ባሳዩት ድራማ ተቀይሞ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይገኝ ይችላል በሚል የተወራ ቢሆንም ከሰሞኑ ክለቡ ሪያልማድሪድ ስለመገኘቱ ማረጋገጫ እንደሰጠ ተዘግቧል፡፡ ብላተር በሜዳ ላይ ወታደራዊ አዛዥ ይመስለኛል ፤ ግዜውን ለፀጉር ሰሪ የሚያባክን ነው፤ ብለው ሮናልዶን እንዳሾፉበት አይዘነጋም፡፡ ሊዮኔል ሜሲ በአጥቂ መስመር ለባርሴሎና እና ለአርጀንቲና ባለፈው የውድድር ዘመን አንስቶ ያሳየው ምርጥ ብቃት ቢደነቅም ከቅርብ ወራት ወዲህ በጉዳት ከጎል አልቢነት መራቁ በምርጫው ተፅእኖ ሊፈጥርበት ይችላል፡፡

የፈረንሳዩ ምርጥ የአማካይ መስመር ተጨዋች ፍራንክ ሪበሪ ከሮናልዶ እና ከሜሲ ጋር ለወርቅ ኳስ ሽልማት ለመፎካከር በእጩነት የገባው ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ባየር ሙኒክ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ የጀርመን ቦንደስሊጋ እና ኤፍኤ ካፕ ሶስት የዋንጫ ድሎችን ያጣጣመው ሪበሪ ፈረንሳይን ለ20ኛው የብራዚል ዓለም ዋንጫ እንድታልፍ ጉልህ ሚና በመጫወቱም አድናቆት አትርፏል፡፡በ2013 ሮናልዶ ለሪያል ማድሪድ ለፖርቱጋል ጎሎች ሲያስመዝግብ ሜሲ ለባርሴሎና እና ለአርጀንቲና 45 እንዲሁም ሪበሪ ለባየር ሙኒክ እና ለፈረንሳይ 21 ጎሎች በማግባት በርቀት ይከተሉታል። የ26 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ በትራንስፈርማርኬት የዝውውር ገበያ 120 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ሲኖረው የ28 ዓመቱ ክርስትያኖ ሮናልዶ የተተመነው በ100 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ የ30 ዓመቱ ፍራንክ ሪበሪ ደግሞ 42 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚያወጣ ተገምቷል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የህፃናት ሩጫው በመሰረዙ በስፖርት ቤተሰቡ እና በህፃናት ላይ ለተፈጠረው መጉላላት ከፍተኛ ይቅርታ ጠየቀ። የህፃናት ሩጫውን ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ ለማካሄድ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም አልተቻለም፡፡ የውድድሩ አዘጋጆች በህፃናት ሩጫው እስከ 250 ተማሪ በማስመዝገብ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረውን ‹‹ፋውንቴን ኦፍ ኖውሌጅ›› ትምህርት ቤት ለማበረታት ዛሬ ልዩ የሩጫ ውድድር እንደተዘጋጀም ተናግረዋል፡፡ 3500 ህፃናትን በማሳተፍ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የህፃናት ሩጫው የአዲስ አበባ ፖሊስ ለልጆች ደህንነት ሲባል እንደሰረዘው ያስታወሱት የውድድሩ አዘጋጆች፤ ዋናው የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በተሳካ ሁኔታ ከተካሄደ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለማድረግ የነበረው ጥረትም አልተሳካም ብለዋል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በህፃናት ሩጫው ለመሳተፍ የተመዘገቡ ሁሉ የመሮጫ ቲሸርታቸውን በመያዝ በለገሃር ቴሌ፤ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቢሮ እና በስታድዬም ዙርያ በሚገኘው ቴድ የስፖርት ትጥቅ መሸጫ ተገኝተው ሜዳልያቸውን መውሰድ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገነባው ሁለገብ የስፖርት አካዳሚ እና የመወዳደርያ ስፍራ 42 በመቶ መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡ ከ530 ማሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚሆንበትን አካዳሚው የሚገነባው አፍሮፅዮን ኮንስትራክሽን ሲሆን አማካሪው ሺጌዝ ኮንሰልታንሲ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የዘንድሮውን የከፍተኛ ትምህርት የስፖርት ፌስቲቫል በዚሁ ሁለገብ የስፖርት አካዳሚና የመወዳደርያ ስፍራ እንደሚያስተናግድም ታውቋል፡፡ የስፖርት ፌስቲቫሉ ከመጀመሩ 10 ቀናት ቀናት ቀደም ብሎ የአካዳሚው የመጀመርያው የግንባታ ደረጃ ይጠናቀቃል፡፡ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል ከየካቲት 1 እስከ 16 ሲከናወን ድረስ 34 ዩኒቨርስቲዎች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በ12 የስፖርት ዓይነቶች የሚካፈሉ ከ6 ሺ በላይ ስፖርተኞች በማሳተፍ ይወዳደሩበታል፡፡

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሁለገቡ የስፖርት አካዳሚና የመወዳደርያ ስፍራ እያስገነባቸው ካሉት የስፖርት መወዳደርያዎች መካከል ሶስትና ሁለት ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችሉ አምስት የእጅና ቅርጫት ኳስ ሜዳዎችን ጨምሮ ሁለት የሜዳ ቴኒስ፣የዋና እና የእግር ኳስ ሜዳ ይገኙባቸዋል። ከእነዚህ 5 የስፖርት መወዳደርያ ሜዳዎች የሁለቱ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የቀሪዎቹ ደግሞ 85 በመቶ የግንባታ ስራው መጠናቀቁ ተገልጿል። በግንባታ ላይ ከሚገኙት የስፖርት መወዳዳርያዎች 25 ሺ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችለው የእግር ኳስ ሜዳ እንዲሁም የሜዳ ቴኒስና የዋና መወዳደርያዎች የግንባታ ስራ 50 በመቶ የተከናወነ ሲሆን እስከ ጥር ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቁ ይጠበቃል፡፡ የሁለገብ የስፖርት አካዳሚና የመወዳደርያ ስፍራ ግንባታው በዩኒቨርሲቲው ለሚሰጠው የመጀመርያና ሁለተኛ ድግሪ የሰውነትና ጤና ማጎልመሻ ትምህርት አገልግሎት የሚውሉ 10 የመማርያ ህንጻዎችም ግንባታን ያካትታል፡፡

አመራሩ ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ አስገብተናል ብሏል 

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ ባልወጣ ህግ እና የባቡር ፕሮጀክቱን ሠበብ በማድረግ፣ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ያቀዳቸውን ሠላማዊ ሠልፎች እንዳይካሄድ መከልከሉን አስታወቀ፡፡ ፓርቲው፤ የሠላማዊ ተቃውሞን መንገድ መዝጋትና የዜጐችን ህገ-መንግስታዊ መብቶች ማፈን በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል፡፡ የመድረኩ አመራሮች በትናንትናው እለት በፓርቲው ፅ/ቤት ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ፤ ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ.ም በኢህአዴግ እየተፈፀሙ ናቸው ያላቸውን ኢ-ሠብአዊና ፀረ ዲሞክራሲያዊ የመብት ጥሠቶችና ህገ-መንግስቱን የሚፃረሩ ህጎችና አዋጆች እንዲሻሻሉ ወይም እንዲቀሩ ለመጠየቅ አዘጋጅቶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ፣ የባቡር ሃዲድ ስራን በማሳበብ መከልከሉን ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ህዳር 8 ቀን 2006 ዓ.ም በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰውን ግፍ ለመቃወም አዘጋጅቶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍም “ፀጥታ የሚያስከብር የፖሊስ ሃይል የለኝም” በሚል ሰበብ በመንግስት እንደተከለከለ መድረኩ ገልጿል፡፡ ለ3ኛ ጊዜ ያዘጋጀውና በአገሪቱ አሳሳቢ ናቸው ያላቸውን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመንግስት ለማሳሰብ፣ ህዳር 29 ቀን 2006 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ፣ እውቅና ሰጪው አካል በይፋ ያልወጣና ገና በህትመት ላይ የሆነን ደንብ በመጥቀስ “የጠየቃችሁበት ስፍራ ሰላማዊ ሰልፍ የማይካሄድባቸው ቦታዎች ተብለው የተጠቀሱ በመሆናቸው፣ ለተጠየቀው ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና መስጠት አንችልም” የሚል መልስ እንደሰጠ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

የፓርቲው የወቅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በሰጡት ማብራሪያ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እየታፈነ በመሆኑ፣ ህዝቡ ብሶቱን ማሰማት የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡ “ሰልፍ በምድር አይቻልም ተብለናል፤ ሰማይ ላይ እናደርግ እንደሆን አናውቅም ያሉት ዶ/ር መረራ፣ በሳውዲ ግፍ ለተፈፀመባቸው ወገኖቻችን እንኳን ብሶታችንን እንዳናሰማ መከልከሉ ኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ግራ እንድንገባ አድርገናል ብለዋል፡፡ የመድረክ አመራር አባል አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው፤ በማይታወቅና ገና ባልፀደቀ ህግ መመሪያ እየተሰጠ መሆኑን አመልክተው፤ “ይህቺ ሃገር በአሁን ሰዓት በህገ መንግስቱ እየተመራች ነው” ብዬ አላምንም ብለዋል፡፡

መንግስት በነዚህ እርምጃዎቹም ብዙዎችን ከሰላማዊ ትግል እንዲወጡና ወደ ጠመንጃ አማራጭ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሌላው የመድረክ አመራር አባል አቶ ገብሩ ገ/ማርያም ፤ የሰላማዊ ሰልፉን መከልከል እንዲሁም ሃገሪቱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የሚያሳስብ ደብዳቤ ሃሙስ እለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግስት ሰላማዊ ሰልፎቹን ከማገዱም በተጨማሪ የዜጎች እንቅስቃሴ በሙሉ ከራሱ ጋር ብቻ እንዲቆራኝ ለማድረግ 1 ለ 5 የሚባል የስለላ፣የቁጥጥርና የአፈና መዋቅራዊ ወጥመድ መዘርጋቱን የመድረክ አመራሮች ገልፀዋል፡፡ በዚህ መዋቅርም በምርጫ ወቅት የዜጎችን ነፃና ሚስጥራዊ የድምፅ አሰጣጥ መብት ለማፈንና ለመጣስ እንዲሁም የእያንዳንዱን ዜጋ ፖለቲካዊ አቋምና አስተያየት፣ የእለት ተእለት እንቅስቃሴውን ጭምር ለማፈን እየተንቀሳቀሰ ነው በማለት “በዚህም ኢህአዴግ የእኛን ድምፅ እያፈነና እንዳንንቀሳቀስ እያደረገ፣ ለራሱ የተጠናከረ የምርጫ ቅስቀሳና ዝግጅት ከወዲሁ ጀምሯል” ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ እንዳንቀሳቀስ አድርጎናል ካላችሁ ቀጣዩን ምርጫስ እንዴት ልትወጡት ነው የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው የመድረኩ አመራሮች፤ ምንም እንኳ ጫናው ቢበረታብንም ውስጥ ለውስጥ ስራችንን እየሰራን ነው፤ነገር ግን እንደዚህ ቀደሙ የምርጫው አጃቢዎች ብቻ ሆነን ለመቅረብ አንፈልግም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የመድረኩ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ፤ የ1ለ5 አደረጃጀት እሳቸው በሚያስተምሩበት ዩኒቨርስቲም መግባቱን አመልክተው፤ ኢህአዴግ አባይ ሣያልቅ ስልጣን አለቅም እያለ ቢሆንም፣ በአንድ ወር ስራ ብቻ በምርጫ ሊሸነፍ የሚችል ፓርቲ ነው ብለዋል።

Published in ዜና

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቢሆንም ግን ፈተናውን ወድቋል የሚሉት አቶ ልደቱ አያሌው፤ የኢኮኖሚ እድገቱን መካድ ስህተት ነው፤ እድገቱ ዘላቂነት እንደሌለው አለመገንዘብም ስህተት ነው በማለት የኢዴፓ “ሦስተኛ አማራጭ” የተሰኘ የኢዴፓ አቋምን ይተነትናሉ፡፡ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከም አንዱ ምክንያት የመንግስት ተጽእኖ እንደሆነ አቶ ልደቱ ገልፀው፤ ነገር ግን ህዝቡን አሰባስቦ በመታገል የመንግስትን ተጽእኖ ማስቆምና ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ይልቅስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ለመፈተሽና ስህተታቸውን ለማረም አለመዘጋጀታቸው ትልቅ እንቅፋት ሆኗል ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ፣ በጭፍን ድጋፍና በጭፍን ተቃውሞ ለሁለት ስሜታዊ ጽንፎች ፖለቲካ እንደሰፈነ ጠቅሰው፤ ስር የሰደደውን የተሳሳተ የጽንፍ አስተሳሰብ በምክንያታዊ አስተሳሰብ በመተካት ሦስተኛ አማራጭ መያዙ ለአገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ይላሉ፡፡ ከ1997 ወዲህ የአገሪቱ ፖለቲካ ቁልቁል እየተንሸራተተ በ15 አመት ወደኋላ መመለሱን ሲያስረዱ፤ አሁንም ከደጡ ወደ ማጡ እንዳይሰምጥ፣ ከዚያም ወደፊት እንዲራመድ ቁልፍ ያለው በገዢው ፓርቲ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በህዝቡ ዘንድ ነው ብለዋል አቶ ልደቱ፡፡ አቶ ልደቱ እነዚሁ 3 ቁልፍ አካላት ካሁን በፊት ምን ስህተት እንደሰሩና ወደፊት ምን እንደሚጠበቅባቸው ከመተንተን በተጨማሪ፤ ለበርካታ ጉዳዮች ላይ የሰነዘሩትን ሃሳብ በዚህ ቃለ ምልልስ እናቀርባለን፡፡

አቶ ልደቱ ለረጅም ጊዜ ጠፍተዋል..ከፓለቲካውም ከሃገሪቱም.. ከመገናኛ ብዙሃን ትንሽ ራቅ ስላልኩ የጠፋሁ ይመስላል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለትምህርት ከኢትዮጵያ ውጪ ነው የነበርኩት፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ከሃያ አምስቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አንዱ ብሆንም፣ በጠቅላላ ጉባኤ ከሊቀመንበርነት ስለወረድኩ የፓርቲው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አልመራም፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ከመገናኛ ብዙሃን ርቄያለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ ፓለቲካ ግን አልራቅኩም፡፡ አሁን ትምህርቴን አጠናቅቄ እዚሁ አገሬ እየኖርኩ ነው፡፡ የነበሩበት ትምህርት ቤት ምንድን ነበር የሚባለው… ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ውስጥ፤ ስኩል ኦፍ ኦሬንታል ኤንድ አፍሪካን ስቴዲስ የሚባል አለ፡፡ እዚያ ነው ዲቨሎፕመንት ስተዲስ ያጠናሁት፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ኢዴፓ ‹‹ሶስተኛ አማራጭ›› የሚል ሃሳብ ይዟል፡፡ ይሄ ሃሳባችሁ ከምን አደረሳችሁ? ‹‹ሶስተኛ አማራጭ›› የምንለውን ነገር በአግባቡ ያለመረዳት ነገር አለ፡፡ እኛም በበቂ ሁኔታ አላስረዳን ሊሆን ይችላል፡፡

ሶስተኛ አማራጭ ሲባል፣ ልዩ የርዕዮተ አለም መስመርን ለመግለጽ ሳይሆን፣ የአቀራረብና የስልት ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፓለቲካ፣ እስከ አሁን ድረስ ሁለት ፅንፍ የያዘ ነው። ሁለትም ነገር መደገፍ ወይም ሁሉንም ነገር መቃወም፡፡ የገዥው ፓርቲ አባል ከተሆነ፤ ተቃዋሚ የሚሰራውን ነገር ሙሉ በሙሉ ማጥላላት፤ የተቃዋሚ አባል ከተሆነ ደግሞ መንግስት የሚሠራውን ነገር ሁሉ መቃወም፡፡ እንዲህ ሁለት ጫፍ የያዘ አሰላለፍ፤ ለአገራችን ፖለቲካ አልጠቀመም፡፡ ከመቻቻል ከመደማመጥ አርቆናል፡፡ ለዚህም ነው፤ ከሁለቱ ጽንፎች የተለየ አማራጭና የተለያየ አቀራረብ ያስፈልጋል የሚል አስተሳሰብ ይዘን የመጣነው፡፡ በመንግስትም ሆነ በተቃዋሚ የተሠራ ነገር ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ከሆነ ልንደግፈው ይገባል፡፡ የማይጠቅምና የሚጐዳ ከሆነ ደግሞ በተጨባጭ መረጃ መቃወምና እንዲቀየር መታገል ያስፈልጋል፡፡ በስሜታዊ ጽንፍ ሳይሆን በምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው ፖለቲካው ሊመራ የሚገባው፡፡ አለበለዚያ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ ዲሞክራሲያዊ የመቻቻል ባህል ሊቀየር አይችልም። ሁለት ስሜታዊ ፅንፎችን ይዞ፣ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው የሚያዋጣን ብለን ሶስተኛ አማራጭ ይዘናል፡፡ ይሄንን አቀራረብ ይዘን ስንመጣ ፈተናዎች ገጥመውናል፡፡

ሁለቱ ጽንፎች ለረዥም ጊዜ ስር የሰደዱና የከረሩ ስለነበሩ፣ ብዙ ሰዎች የእኛን አስተሳሰብ ለመቀበል በጣም አስቸግራቸዋል፡፡ ደግሞም አያስገርምም፡፡ ሰዎች በቀላሉ ይሄን አስተሳሰብ የሚቀበሉ ከሆነ፤ ከመነሻው የአገራችን ፖለቲካ ከባድ ችግር የለበትም ማለት ነው፡፡ የአገራችን ፖለቲካ ግን ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ትልቅ ችግር አለበት፡፡ ስለሆነም፤ ሦስተኛ አማራጭ ብለን ያቀረብነው የምክንያታዊ አስተሳሰብ አቅጣጫችንን ብዙ ሰዎች በቀላሉ ሊቀበሉት አልቻሉም። “ተቃዋሚ ከሆንክ በቃ ማንኛውንም ነገር ትቃወማለህ፡፡ ኢህአዴግም ከሆንክ ማንኛውንም ነገር ትደግፋለህ፤ ሌላ ሦስተኛ አማራጭ የለም” የሚል የተዛባ አመለካከት ይሰነዘርብን ነበር፡፡ “እንዲያውም ሦስተኛው አማራጭ የምትሉት ነገር ወላዋይነት ነው” በማለት ውዥንብር የመፍጠር ነገርም ነበር። በሂደት ግን፣ ብዙ ሰው ጉዳዩን እያብላላው፣ እያጤነውና እየተገነዘበው እንደሆነ አይተናል፡፡ እኛ በምንፈልገው ፍጥነት ህብረተሰቡ ተረድቶታል የሚል እምነት የለንም፡፡ ገና ብዙ ይቀራል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስከአሁን በመጣበት የጽንፈኝነት መንገድ የትም ሊያደርሰን እንደማይችል ብዙዎች እየገባቸው ነው፡፡ ሁለቱ ጽንፎች የሚፈጥሩት ቅራኔና ውጥረት፣ ከዴሞክራሲ እያራቀን እንጂ ወደ መቻቻል እያመጣን እንዳልሆነ ሰው እየተገነዘበው ነው፡፡

“ሁለቱ የፅንፍ ሃይሎችና ጐራዎች አይጠቅሙም ትክክል አይደሉም” የሚለው አስተሳሰብ እየጐላ መጥቷል፡፡ “ሁለቱም ፅንፎች አይጠቅሙም፤ ችግር አለባቸው” ከተባለ ክፍተት መኖሩን ነው የሚያሳየው፡፡ ያንን ክፍተት የመሙላት ጉዳይ ነው የሶስተኛው አማራጭ ፋይዳ፡፡ ይሄንን አስተሳሰብ ይዘን እንደነበር በተለይ በፓርላማ በነበረን ተሳትፎ በደንብ ማሳየት ችለን ነበር፡፡ ፓርላማ ውስጥ ሌሎች ተቃዋሚዎች ከሚያራምዱት አስተሳሰብ በተለየ ሁኔታ፣ መንግስት ከሚሠራቸው ነገሮችና ከሚያራምዳቸው አቋሞች ውስጥ ለህዝብና ለሀገር የሚጠቅም ነገር ስናገኛቸው በድፍረት ስንደግፍ ታይቷል፡፡ ሰው ለዛ የሚሠጠው ትርጉም ምንም ይሁን እኛ ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማል ብለን እስካመንበት ድረስ በድፍረት ወጥተን፤ ይሄ አቋም ከገዢው ፓርቲም ይምጣ ከተቃዋሚ ፓርቲም ይምጣ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ እንደግፋለን ብለን ማሳየት ችለናል፡፡ ገዢው ፓርቲ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን ሲሰራ ደግሞ ከሌሎች ተቃዋሚዎች በበለጠ በመረጃ በተደገፈ ከመተቸትና በጠነከረ መልኩ በመታገል ምክንያታዊነታችንን ማሳየት ችለናል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥም ጥፋት ወይም ድክመት ሲኖር፣ ተቃዋሚ ነውና እሱን አንነካውም አንልም፡፡ እንዲስተካከል እንተቻለን፡፡ ለሰላማዊ ትግልና ለአገር የማይበጅ፣ ለመቻቻል ፖለቲካ ማይጠቅም ሆኖ ካገኘነው፣ ተቃዋሚውንም ቢሆን በድፍረት የመተቸት አዲስ ባህል ይዘን መጥተን አሳይተናል፡፡ ያን የማይወዱ ሰዎች ብዙ ነበሩ፡፡

በሂደት እየተረዱ ሲመጡ፣ ግን እኛ የያዝነው አቋም ትክክል እንደሆነ መገንዘብ የቻሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይሄ አቋማችን በአገራችን ያልተለመደ አዲስ አቋምና አካሄድ ስለሆነ፤ አንዳንድ ሰዎች በእኛ ላይ የሚያወሩትን አሉባልታ ማራገብ ተጠቅመውበታል። በእኛ ላይ ከንቱ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲስፋፋ በማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፈዋል። በሌላ በኩል ግን ከነባሩ የጽንፈኝነት ፖለቲካ የተለየ ምክንያታዊ ፖለቲካ ማራመድ ለዚህ አገር እንደሚያስፈልግ በደንብ ለማሳየት ችለናል፡፡ ስለዚህ ሦስተኛ አማራጭ ይዘን መምጣታችን፣ ጥቅምም ጉዳትም ነበረው፡፡ ከአጭር ጊዜ አንፃር፣ ሊያስወድድ የሚችል የፖለቲካ አቋም አልነበረም፡፡ ለአሉባልታ አጋልጦናል፡፡ ከረጅም ጊዜ አንፃር ግን ይሄ ምክንያታዊ የፖለቲካ መስመራችን እየሰፋና እያደገ፣ በተለይ በአዲሱ ትውልድ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የሚመጣ አቋም ነው፡፡ ስለዚህ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ እየተጠናከረ ነው፡፡ ግን ሂደቱን እኛ ስለተናገርነውና ስላራመድነው ብቻ ውጤት ያመጣል ማለት አይደል፡፡ ከአጠቃላይ ከአገራቱ ሶሽዬ ኢኮኖሚክ የእድገት ደረጃ ጋር ተያይዞ ነው ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወጥቶ ስለተናገረ ብቻ፣ የበቃ የፖለቲካ አመለካከት ያለው ህብረተሰብ ይፈጠራል ማለት አይደለም፡፡ እንደዛ አይነት ህብረተሰብ የሚመጣው ኢኮኖሚያችን ሲያድግና ሲዳብር፤ ትምህርት ሲስፋፋና ከሌላው አለም ጋር መስተጋብራችን የበለጠ ሲጠናከር ነው፡፡ በአጭር ጊዜ የሚቀየር ነገር አይደለም፡፡

የአስተሳሰብ ለውጥ እውን የሚሆንበት ሂደት በጣም የተራዘመ እንዳይሆንና እንዲፋጠን በማድረግ ረገድ ግን የኢዴፓ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ እንግዲህ መንግስት ኢኮኖሚው በደብል ዲጂት እያደገ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የህብረተሰቡ ኑሮ ግን መንግስት ከሚገልፀው የተለየ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ? ኢኮኖሚውን በሚመለከት፣ የኛ አመለካከት ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይለያል፡፡ በመጀመሪያ እድገት አለ ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን መንግስት ሁሌም በሚናገረው መጠን ደብል ዲጂት እድገት አለ ብለን አናምንም፡፡ አንዳንድ አለማቀፍ ድርጅቶች እንደሚገልፁት እድገቱ ወደ ስምንት ሰባት ፐርሰንት አካባቢ ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን፡፡ አቅሙን ለመናገር የሚያስችል በቂ መረጃ በእጃችን የለም፤ ሊኖረንም አይችልም፡፡ ነገር ግን ከአጠቃላይ ግንዛቤ ተነስተን ስናየው፤ መንግስት ከበታች አካላት እያገኘ ያለው መረጃ ትክክል ነው ብለን አናምንም፡፡ በብዙ ምክንያቶች የተዛባ መረጃ ነው ከታች ወደ ላይ የሚመጣው፡፡ የሚመጣውን ዳታ አምኖ መቀበል ያስቸግራል፡፡ በዚህ ምክንያት ፓርላማ በነበርኩበት ጊዜ፣ የመረጃ ምርምራ ወይም ኦዲቲንግ ሲስተም ያስፈልገናል እል ነበር፡፡ የገንዘብ እና የአሠራር ኦዲቲንግ ብቻ ሳይሆን የመረጃዎች ትክክለኛነት ለመፈተሸ ኦዲት መደረግ አለበት የሚል ሃሳብ ስናነሳ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ይሄን ሃሳብ የሚቀበለን አልነበረም፡፡ አሁን ግን መረጃዎችን ኦዲት ማድረግ አለብን የሚል ሃሳብ በመንግስት እየተነሳ እያየን ነው፡፡ ይሄ የኢኮኖሚ እድገት አለ የሚባለው፡፡ መኖሩ ጥር ጥር የለውም፡፡ በምን ይገለፃል? ስለመኖሩ ህብረተሰቡ ውስጥ የምናያቸው እንቅስቃሴዎች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የልማቱን እንቅስቃሴ እንውሰድ፡፡ በመንግስት በኩል ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እየፈሰሰ መሠረተ ልማት እየተስፋፋ ነው፡፡ ይሄ በየትም አገር ቢሆን የኢኮኖሚ እድገትን ያመጣል፡፡ የግሉ ክፍሉ ኢኮኖሚ ከድሮ በተሻለ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍም በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ከፍተኛ የግንባታ እንቅሰቃሴ አለ፡፡ እንዲያም ሆኖ እድገቱ ሙሉ በሙሉ ጤናማ ነው ማለት አይደለም፡፡ ችግሮች የሉበትም ማለት አይደለም፡፡ ዕድገቱ መንግስት በሚለው መጠን ነው ማለት አይደለም፡፡

የእድገቱ መጠን መንግስት እንደሚለው ሳይሆን፣ ስምንትና ሰባት ፐርሰንት ይሆኖል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄም ቢሆን መጥፎ እድገት አይደለም፤ ጥሩ እድገት ነው፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ደረጃ ላለ ድሃ አገር ከስድስት ፐርሰንት በታች የወረደ እድገት፤ ኢኮኖሚው እንደተኛ (ሪሴሽን ውስጥ እንደገባ ነው የሚቆጠረው፡፡ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ማደግ ነው የሚጠበቅብን፡፡ የሌሎችም አገራትም ታሪክ ያንን ነው የሚያሳየው፡፡ እንደ አሜሪካና እንደ እንግሊዝ አገር አይነት ትልቅ ኢኮኖሚ ውስጥ ሶስትም አራትም ፐርሰንት ማደግ ከባድ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ኢኮኖሚ ተይዞ ግን፤ ደብል ዲጂት ማደግ ይቻላል፡፡ መጣ የሚባለው እድገት በህብረተሰቡ ህይወት ውስጥ መታየት አልነበረበትም ወይ? ሊታይም ላይታይም ይችላል፡፡ አንድ ኢኮኖሚ ማደግ ሲጀምር ሁሉንም ህብረተሰብ ይጠቅማል ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ በየትም አገር ሆኖ አያውቅም፡፡ እንኳን ዘጠና ሚሊዬን ህዝብ ያለበት አገር ይቅርና፣ 3ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገርም ኢኮኖሚው ማደግ ሲጀምር ሁሉም ህብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ቀስ በቀስ ነው ተጠቃሚው እየበረከተና እያደገ የሚመጣው፡፡ ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ድህነት ይታያል። ድህነት ብቻ አይደለም በርሃብም የሚሰቃዩ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መኖራቸው ግን እድገት የለም ወደሚለው ድምዳሜ አይወስደንም፡፡ እድገትም ባለበት አገር ሰው ይራባል፤ ሰው በድህነት ይማቅቃል፡፡ እንኳን በእኛ በጀማሪ አገር ቀርቶ፣ የዳበረ እድገት አላቸው የሚባሉ አገሮችም የሚቸገሩ ሰዎች አሉ፡፡

እነዛ ሰዎች ስላሉ ግን ያ አገር አላደገም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የካፒታሊስት (የነፃ ገበያ) ስርዓት ውስጥና በአንድ ጊዜ ሃብት በእኩል መጠን ሊዳረስ አይችልም፡፡ በሂደት ነው፡፡ እንግዲህ የመንግስት ሚና እዚህ ላይ ነው የሚጠበቀው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እድገት መኖሩ ጥርጥር የለውም፡፡ ዋናው ችግር ሌላ ነው። አሁን የምናየው እድገት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ መሠረታዊና መዋቅራዊ ለውጥ ሚያመጣ ነው ብዬ አላምንም ዘላቂነት የለውም፡፡ አሁንም የዝናብ እርሻ ጥገኛ ነኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ኢኮኖሚ ዘላቂ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይ ማኑፋክቸሪንግ ተረስቶ ነው የኖረው፡፡ እኛ ለኢንዱስትሪው ትኩረት መስጠት እንዳለበት ስንናገር አይቀበሉንም ነበር፡፡ በእርግጥ ለእርሻው ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ የግድ ነው፡፡ ሰማንያ በመቶ ህዝብ በእርሻ ላይ ጥገኛ ሆኖ እርሻውን መዘንጋት አይቻልም፡፡ ግን በተመሳሳይ ሁኔታ ለኢንዱስትሪውም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ፤ ኢኮኖሚው በየዓመቱ ከእርሻ ጥገኝነትን ወደ ኢንዱስትሪው እስካልተሸጋገረ ድረስ፣ የኢኮኖሚ እድገቱ ዘላቂነት አይኖረውም፡፡ በዚህ ከተመዘነ የአገራችን ኢኮኖሚ ፈተናውን ወድቋል፡፡ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ወዲህ የገበሬ መጠን ምን ያህል ቀነሰ ብትይ፣ ከሶስት ፐርሰንት በላይ አልቀነሰም፡፡ አሁንም የእርሻ ጥገኛ ነን፡፡ አጭሩ መዋቅራዊ የሆነ ለውጥ አላመጣም፡፡ ግን እድለኞች ሆነን፣ በአለፉት ዘጠኝና አስር ዓመታት ጥሩ ዝናብ አለ፡፡ ይሄ ዝናብ ቢቋረጥ የምናወራለት የኢኮኖሚ እድገት እንክትክት ብሎ ነው የሚወድቀው፡፡ ለፓርቲው ስራ እና በትምህርት ወደ ውጭ አገራት ሲጓዙ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ስለአገሪቱ ፖለቲካና ወቅታዊ ጉዳይ ይወያያሉ? በተለያየ አጋጣሚ ውጭ አገር ሄጄ የኢትዮጵያውያንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማየት ለማታዘብ እድል አግኝቻለሁ፡፡

በደፈናው ውጭ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲህ ነው ብሎ ለመፈረጅ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ዓይነት ነው፡፡ ዝም ብሎ ስራውን የሚሠራ አለ፡፡ ገባ ወጣ የሚል አለ፡፡ አገር ቤት ገብቶ ብዙ ስራ የሚሠራ አለ፡፡ ከኢትዮጵያ ከወጣ የሰላሳና የአርባ ዓመት የቆየ አለ፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት ሄጄ ተመልሻለሁ፡፡ ከፓለቲካው የራቀ አለ፡፡ አይነቱ ብዙ ነው፡፡ በውጭ አገር የለው ተቃዋሚ ሃይል እየሰራው ያለው ፖለቲካ ግን በአብዛኘው ለአገር የሚጠቅም አይደለም፡፡ የነሱ ተፅዕኖ ባይኖር፣ እዚህ አገር ያለው ፖለቲካ የተሻለ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ የዳያስፖራ ፓለቲካ፣ የአገሪቱን ፓለቲካ ወደ ጽንፈኝነት የሚገፉ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሆነ አገሪቱን እየጠቀማት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲበላሽ፣ ወደ ፅንፍ የከረረ አቅጣጫ እንዲሄድ የማድረግ አዝማሚያ ነው የማየው፡፡ ግን ኢዴፓን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች በአሜሪካ በአውሮፓ አላችሁ፡፡ አይደለም? አዎ ኢዴፓ በውጭ አገራት ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ አለን፡፡ ነገር ግን እዚያ ያለው መንፈስ እንከተላለን ማለት አይደለም፡፡ አገር ውስጥ ያለው ሁኔታና በዳይስፖራ ተቃውሞ የሚያስተጋባው ነገር በጣም የተራራቀ ነው፡፡ እነሱ የሚሉትን ከሰማሽ፤ እዚህ አገር አንድ ሰው በጠዋት ከቤቱ ወጥቶ ማታ በሰላም ይመለሳል ብለሽ አታስቢም፡፡ ሰው ስራ ሰርቶ እንጀራ በልቶ ይኖራል ብለሽ አታስቢም፡፡ ይሄ ሲባል ግን፣ ሁሉም አንድ ዓይነት አስተሳሰብ አላቸው ማለት አይደለም፡፡ እንዲያው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዳይስፖራ ከፖለቲካው ርቆ የሚኖር ነው፡፡ ‹‹ሳይለንት ማጆሪቲ›› እንደሚባለው ዓይነት ነው፡፡

በፖለቲካው በጣም ገንነው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ከአገር ከወጡ ብዙ ዓመት የሆናቸውና አንዳንዶቹ ሆን ብለው ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ነገር አይፈጠርም ተብሎ ማውራት ተገቢ ይመስላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተተረማመሰች ብሎ መናገር ይጠቅመናል ብለው የሚያስቡ ሰዎችም አሉ፡፡ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችልና የሚገባው የዳይስፖራው ማህበረሰብ አሁን እያደረገ ያለው ነገር በጣም ጐጂ መሆኑን ተገንዝቦ ይሄን ነገር መለወጥ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች በቀላሉ የሚለወጡ ናቸው ማለት ይከብዳል። ካልተለዋወጡ ግን ህዝቡ ስለነሱ ያለውን ግምት መለወጥ ይችላል፡፡ ‹‹ውጭ አገር ያለ ፖለቲከኞች የተማሩ፣ ገንዘብ ያላቸው፣ ዲሞክራሲ ባለበት አገር የሚኖሩ ናቸው ስለዚህ ከአገራችን ጥሩ ነው የሚያስቡት፤ እውቀት አላቸው›› ብሎ ማሰብ በራሱ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምን ያህል ፖለቲካችንን እየጐዳው እንዳለ እንቅስቃሴያቸውን መገንዘብ አለበት፡፡ ዛሬ ዛሬ የፓርላማ ስብሰባዎችን ሲመለከቱ ምን ይሰማዎታል? አንድ የተቃዎሚ ፓርቲ ተመራጪ ብቻ ናቸው፤ በፓርላማ ውስጥ የሚታዩት? እውነት ነው፡፡ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በፊት አስራ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮች ፓርላማ ውስጥ ነበሩ፡፡ በ1997 ዓ.ም. የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ወደ ሰማኒያ ያህሉ ፓርላማ ገብተዋል፡፡ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ሁላችንም ተጠራርገን ወጣን፤ የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ብቻ ነው የቀረው፡፡ ይሄ የሚያሳየው የአገሪቱ የዲሞክራሲ ሂደት ከመሻሻል ይልቅ የኋሊት መመለሱን ነው ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የተቃዋሚው ጐራ በሂደት እየተጠናከረ ከመምጣት ይልቅ እየተዳከመ መምጣቱን ነው የሚያሳየው፡፡ በዋናነት በ1997 ምርጫ ከተሠራው አጠቃላይ ስህተት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ ምህረት የለሽ ሆኖ በሃይል የማፈን ጥረት አደረገ፡፡

በሌላ በኩል አብዛኛው የተቃዋሚ ጐራ፣ ህዝብ የጠሰውንና እጁ ውስጥ የገባውን የምርጫ ውጤት ይዞ በአግባቡ እየተጠቀመ መቀጠል ሲገባው፣ ፓርላማ አልገባም ብሎ ህብረተሰቡን በምርጫ ሂደት ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጎታል፡፡ ያኔ በቅንጅት ፓርቲዎች መካከል ቅራኔ ሲፈጠር፤ የአዲስ አበባ አስተዳደርን እንረከብ፤ ‹‹ፓርላማ አንገባም›› በሚለው ውሳኔ የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ሂደት የኋሊት ለአስራ አምስት ዓመት የሚመልስ ስህተት መሆኑን ገልጸን ነበር፡፡ በዚያ ስህተት ሳቢያ ነው ዛሬ ዋጋ እየከፈልን ያለነው፡፡ ያኔ በአግባቡ ያገኘነውን የፓርላማ ወንበር ተረክበን፤ የአዲስ አበባ አስተዳደርንም ተረክበን በመስራት ህዝቡን ከነስሜቱ ይዘን ብንቀጥል፤ ኖሮ እስከአሁን መንግስት የመሆን እድል ይኖረን ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ያኔ የኛን ሃሳብ መስማት ያልፈለጉ ጎራዎች፤‹‹ መንግስትን በሁለት እና በሶስት ወር እንጥለዋለን፤ ዕድሜ የለውም›› ብለው ነበር የሚናገሩት፡፡ ኢህአዴግ አልቆለታል፤ ነበር የሚሉት። ታሪካዊ ስህተት ነው የተፈፀመው፡፡ አሁንም ቢሆን፣ ተቃዋሚው ጎራ በነገሩ የፅንፍ ፓለቲካ የሚንዙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ሌላ 15 ዓመት ወደኋላ ይሄዳል፡፡ ኢህአዴግ ወደፊት ለሃያና ለሰላሳ ዓመት በስልጣን ላይ የመቆየት እድል ያገኛል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ፣ ይሄንን አለን፡፡ አሁን እየታየ ያለው አሳዛኝ የፓለቲካ ሁኔታ ለእኛ አዲስ አይደለም፤ ያኔ የተሠራው ስህተት ውጤት ነው፤ የዘራነውን እያጨድን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እያደገ መሄድ ሲገባው ወደኋላ እየሄደ ነው፡፡ ይሄ ለገዥው ፓርቲ ሆነ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቅ ሽንፈት ነው፡፡ የአገር ሽንፈት ነው፡፡ በዚህ ማንም መደሰት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በኋላ ተቃዋሚዎች በቀጣዩ ምርጫ ራሳቸውን አጠናክረው መምጣት ይችላሉ? ተቃዋሚው ጎራ ራሱን እንዲያሻሽልና እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚገባቸው ሶስት አካላት አሉ፡፡ መንግስት፣ የዲሞክራሲ ሂደቱ የበለጠ እንዲፋፋ አፋዊ ሳይሆን ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ በአብዛኛው ስለ ዲሞክራሲያዊ ሂደት መንግስት እየተናገረ ያለው አፋዊ ነው በተግባር የሚገለፅ አይደለም፡፡ ወረቀት ላይ ይቀመጣል፡፡ በቲቪና በሬዲዮ ሲነገር እንሰማለን፡፡ በተግባር ግን የሚሠራው ከዛ የተለየ ነው፡፡

ሁለተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቆም ብለው ማሰብ አለብን፡፡ “የህዝብ ድጋፍ የለውም” የምንለውን ኢህአዴግን ለ22 ዓመታት ታግለን ለውጥ ያላመጣነው ለምን እንደሆነ ቆም ብለው በሃቅና በድፍረት ራሳችንን መመርመር ካልቻልነው፤ ከዛ ሂደት ተምረን መሠረታዊ የሆነ የአካሄድ ለውጥ እስካላደረግን ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊቀየር አይችልም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመጠናከር ይልቅ በተቃራኒው እንደውም በሂደት እየተዳከምን የመጣነው ለምንድን ነው? እውን ይሄ የሆነው በኢህአዴግ ተጽዕኖ ብቻ ነው ወይ? የራሳችን የውስጥ ችግር፤ ድክመት፣ ስህተት የለብንም ወይ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች እነዚህን ጥያቄዎች መርምረንና ራሳችንን ፈትሸን ራሱን ገምግሞ መሠረታዊ የመፍትሄ ሃሳብ ይዘን ካልመጣን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይሻሻላል ብዬ አላምንም፡፡ ኢዴፓ ይንንን ሃላፊነት ለመወጣት የድርሻውን እየሰራ ነው፡፡ በርካታ ተቃዋሚ ወገኖች ግን ራሳቸውን ለመፈተሽ ዝግጁ አይመስለኝም፡፡ በድፍረት መናገር የምችለው፣ ከኢዴፓ በስተቀር ‹‹እኔ ስህተት አለብኝ፤ እስከአሁን የመጣንበት ጉዞ ስህተት ነበረበት፡፡ ያ ስህተት ነው ደካማ ያደረገን›› ብሎ የገመገመ ሌላ ፓርቲ ያለ አይመስለኝም፡፡ አብዛኛው ተቃዋሚ ‹‹እኛ ስህተት የለብንም፤ ሁሌም ስህተት የሚፈጥረው ከገዢው ፓርቲና ከሌሎች ነው›› ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ራሱን ገምግሞ ተገቢ የመፍትሔ ሃሳብ የማያመነጭ ተቃዋሚ፣ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሂደት ላይ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ለራሱም፣ ለሀገሩም አይሆንም፡፡ ሶስተኛው አስተዋፅዖ ከህዝብ ነው የሚጠበቀው። ምክንያቱም ህዝብ ነው የጉዳዩ ባለቤት፡፡ እኛ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳታፊዎች ነን፡፡ የጉዳዩ ዋና ባለቤት ግን ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል፤ ለውጥ የሚመጣው ግን የዳር ተመልካች በመሆን አይደለም፡፡ ገዢው ፓርቲና፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡

ህብረተሰቡም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ተቃዋሚዎች ተጠናክረው እንዲወጡ የሚፈልግ የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ ግን ፍላጎት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ህብረተሰቡ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ስህተቶችን በአግባቡ ማወቅና እንዲታረሙ መታገል አለበት፡፡ ተቃዋሚ ስለሆኑ ብቻ በአዘኔታና በርህራሄ ‹‹ተቃዋሚዎች ናቸውና መተቸት የለባቸውም›› ማለት የለበትም፡፡ ፓርቲዎች ስህተት ሲሰሩ ካየ፣ ህብረተሰቡ መንግስትን ተቃዋሚዎችንም እየተቸ እንዲስተካከሉ ማገዝ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህዝብ የመነጨ ስለሆነ ህብረተሰቡ በገንዘብና በእውቀት ካልረዳቸው በስተቀር በሆነ ተአምር ተጠናክረው ሊወጡ አይችሉም፡፡ የህዝቡ መገለጫዎች ናቸው ስለዚህ ህብረተሰቡ ተቃዋሚዎች እንዲጠነክሩ የሚፈልግ ከሆነ፣ በተግባር አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው የአገራችንን ፖለቲካ ወደተሻለ ደረጃ ሊያደርስ የሚችለው፡፡ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ገዢው ፓርቲ ያወጣቸው አዳዲስ ህጐች አሉ፡፡ የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የፕሬስ ህጉ፤ የፓርቲ ምስረታ አዋጅ፣ የኤንጂኦ ህግ ተቃዋሚዎችን ለማዳከም ገዢ ፓርቲ የፈጠረው ጫና ነው የሚል አስተያየት በስፋት ይደመጣል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ? በአንድ በኩል፤ አዎ መንግስት እየፈፀመ ያለው ድርጊት፤ እያወጣቸው ያሉ ፖሊሲዎችና ህጎች፣ ለተቃዋሚ ጐራ መዳከም የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ብቸኛ ምክንያቶች ናቸው ማለት ግን አይደለም። ራሱ የተቃዋሚ ጐራ ችግሮችም ለሱ መዳከም ምክንያት መሆኑን ቀደም ብዬ ጠቅሼዋለሁ፡፡ ገዢው ፓርቲ ውስጥ የምናያቸው፣ የጭፍን ስሜታዊነት፣ የሙስና፣ የዘረኝነት፣ የአምባገነንነት፣ ችግሮች፤ ሳይቀነሱ ሳይደመሩ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥም እናያቸዋለን፡፡ ገዥው ፓርቲ የሚጎድለው ዲሞክራሲያዊ ባህሪ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጎድሎ ይታያል፡፡

ስለዚህ መንግስት የሚፈጥረው ጫና ለተቃዋሚዎች መዳከም አንድ ምክንያት ነው እንጂ ብቸኛ ምክንያት አይደለም፡፡ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ እኮ ጠንካራ ነው የሚባለው፤ መንግስት የሚያደርግበትን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ማሸነፍ ሲችል ነው፡፡ መንግስት ተጽእኖ የማያደርግ ከሆነማ ሁሉን ነገር የተመቻቸ ከሆነማ ትግልም አያስፈልግም። አገራችን እንደ አሜሪካ ሆናለች ማለት ነው። መንግስት ተፅዕኖ የማያደርግ ከሆነ፣ በጣም የምንመኘው ደረጃ ላይ በቀላሉ ደርሰናል ማለት ነው፡፡ ተዝናንተን በምዕራቡ ዓለም እንደምናየው በምርጫ እየተወዳደርን አሸናፊና ተሸናፊ ልንሆን እንችላለን ማለት ነው፡፡ ግን እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ቀርቶ ጨርሶ አልተጠጋንም፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ጫና የሚያደርግ መንግስት ነው ያለን፡፡ ይህን ለመለወጥም ነው የፖለቲካ ትግል እያካሄድን ያለ፡፡ ህዝቡን አስተባብረንና አታግለን፤ የመንግስት ጫና እንዲቆምና ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ እንችላለን፡፡ ይልቅስ ትልቅ እንቅፋት የሆነብን ውስጣዊ ችግር እንዳለብን መገንዘብ አለማቻላችን ነው፡፡ ውስጣዊ ድክመቶችን ለመፈተሸ አለማድረጋችን ነው ካንሠር ሆኖ የሚበላን፡፡ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ተቃዋሚዎች ጥምረት እየፈጠሩ የህዝቡን ትኩረት በመሳብ በምርጫ ውጤት አምጥተዋል፡፡ የፓርቲዎችን ብርቱ ፉክክር የሚያካሂዱበት ነፃነት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ለ2007 ዓ.ም ምርጫ ግን ጥምረት የመፍጠር ህዝቡን የማንቀሳቀስና ብርቱ ፉክክር የማካሄድ ሁኔታ ጎልቶ አይታይም፡፡ ኢዴፓስ ለቀጣዩ ምርጫ ምን ያስባል? በቀጣዩ ምርጫ መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ አንደኛ ነገር ገዢው ፓርቲ ከስህተቱ እየተማረ አይደለም፡፡ አሁንም በየቀኑ የሚነግረን፤ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ሞልቶ እንደተትረፈረፈና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ለማድረግ ምንም ችግር እንደሌላቸው ነው፡፡ ይህቺ አገር በልማት ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲም እያደረገች እንደሆነ ነው ኢህአዴግ የሚነግረን። ይሄ ቀልድ ነው፡፡ በተጨባጭ ያለው ሁኔታ ኢህአዴግ እንደሚለው አይደለም፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት በአግባቡ በዚች አገር እንዲያብብ እያደረገ አይደለም።

ገዢው ፓርቲ ላይ ቁርጠኝነት እየታየ አይደለም፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩልም አብዛኛው ውስጣዊ ድክመታቸውን ሳይፈትሹ ነባሩን አስተሳሰብና አቀራረብ እንደያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ በ2007 ዓ.ም ምርጫ፣ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ መሠረታዊ ለውጥ ቢመጣ የሚችለው እነዚህ ሁለት ጐራዎች ከስህተታቸውና ከችግራቸው ተምረው የተግባር ማሻሻያዎችን ሲያደርጉ ነው። ይሄን ሲያደርጉ አይታይም፡፡ አሁን የቀረው አንድ ዓመት ነው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ መንገዳቸውን ካላስተካከሉ፣ ምርጫው ከአለፉት ምርጫዎች የተሻለ ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡ በሌላ በኩል አብሮና ተቀናጀን የመስራት ፍላጎት ቢኖር ኖሮ ያለ ጥርጥር የተሻለ ነገር መስራት ይቻል ነበር፡፡ ተቃዋሚው ጎራ እርስ በርስ ተቻችሎ እንዲሰራ የሚያደርግ ሃይል ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡ አቶ ልደቱ በሚቀጥለው ሳምንት፣ ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት ወዲህ ያለውን የኢህአዴግ፣ የመንግስትና የአገሪቱን ሁኔታ ይተነትናሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሦስት ዋና ዋና ፈተናዎች ምን እንደሆኑ በመዘርዘር የመፍትሔ ሃሳቦችን ያቀርባሉ። የአረቡን አለም አዝማሚያዎችንና የግብጽና የአባይ ጉዳዮችን እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ስደትን በተለከተም አቶ ልደቱ ሃሳባቸውን ይገልፃሉ፡፡

14 ህፃናት ተማሪዎችን አሳፍሮ ከጎተራ ወደ ካቴድራል ትምህርት ቤት ይጓዝ በነበረ ኩምቢ ቮልስ መኪና ላይ ባልታወቀ ምክንያት በተነሳ እሳት ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን በህፃናቱ ላይ ምንም አይነት አደጋ አለመድረሱ ታውቋል፡፡ ጎተራ ማሳለጫ ላይ ከመኪናው የፊት አካል የተነሳውን እሳት የተመለከተው ሹፌሩ፤ ልጆቹን ፈጥኖ ከመኪናው በማውጣቱ በህይወት ላይ አደጋ አለመድረሱን የጠቆመው ፖሊስ፤ መኪናው በምን ምክንያት ለእሳት ቃጠሎ እንደተዳረገ የቂርቆስ ፖሊስ መምሪያ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡ እሳቱ በምን እንደተነሳ የተጠየቀው ሹፌሩ፤ እሱም ምክንያቱን እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡ ስለ አደጋው ያነጋገርናቸው የእሳትና ድንገተኛ አደጋ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ በበኩላቸው፤ መኪናው 8 ሰው ብቻ መጫን ያለበት ቢሆንም 14 ህፃናት አሳፍሮ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ እሳቱን ለማጥፋት ከ25 ሺህ ሊትር በላይ ፈሳሽ እንደፈጀና መኪናው በቃጠሎው ከጥቅም ውጭ እንደሆነ አቶ ንጋቱ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና
  • በአቃቤ ህግ ማስረጃ ቀርቦባቸዋል የተባሉ18 ተከሳሾች መከላከያ እንዲሰሙ ተበይኗል

“ድምፃችን ይሰማ” ከተሰኘው እንቅስቃሴና በአወሊያ ት/ቤት መነሻነት ከተፈጠረው መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ በ28 ሰዎች ላይ ላይ የቀረበው የሽብር ክስ፣ በዝግ ችሎት የምስክሮች ቃል ሲደመጥ የከረመ ሲሆን፣ ሀሙስ እለት በተሰየመው ችሎት የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሃቢባ መሃመድን ጨምሮ 10 ተከሳሾች በነፃ እንዲሠናበቱ፣ 18 ተከሳሾች ደግሞ እንዲከላከሉ ተበየነ፡፡ በክስ መዝገቡ የተካተቱት፣ “አልበር ዴቬሎፕመንት ከኦፕሬሽን አሶሴሽን” እና “ነማኢ የበጐ አድራጐት ማህበር” የተሠኙት ሁለት ድርጀቶችም ከክሱ ነፃ ሆነዋል፡፡ ተከሣሾቹ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለወንጀል አድማ ተስማምተው በህገ መንግስት የተደነገገውን የእምነት ነፃነት ጥሰዋል በማለት ክስ ያቀረበው አቃቤ ህግ፤ ከራሣቸው አክራሪ አስተምህሮ ውጭ ሌላ እምነት እንዳይኖር በማለት የሽብር ተግባር ውስጥ ተሣትፈዋል ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ እስላማዊ መንግስት ለማቋቋምም ወደ ተለያዩ የአረብ ሃገራት ሄደው ስልጠና ወስደዋል የሚለው አቃቤ ህግ፣ ተከሣሾቹ አላማቸውን ለማሣካት “የሃይማኖት አስተማሪዎች” እና “የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” በሚል ተደራጅተው ተንቀሣቅሰዋል በማለት ማስረጃ ይሆኑኛል ያላቸውን ምስክሮች አቅርቧል፡፡ ፍ/ቤቱ፣ የምስክሮችን ደህንነት ለመጠበቅ ቃላቸው በዝግ ችሎት እንዳደመጠ ገልፆ፣ ከትናንት በስቲያ ብይን ሰጥቷል፡፡ አቡበከር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል መሃመድ፣ ያሲን ኑሩ፣ ከሚል ሸምሱ፣ በድሩ ሁሴን፣ ሼህ መከተ ሙሄ፣ ሣቢር ይርጉ፣ መሃመድ አባተ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ አቡበከር አለሙ፣ ሙኒር ሁሴን፣ ሼህ ሠኢድ አሊ፣ ሙባረክ አደም እና ካሊድ ኢብራሂም ላይ ቀደም ሲል የተመሰረተው ክስ፣ የሽብር ተግባር ፈፅመዋል የሚል እንደነበረ ፍ/ቤቱ ጠቅሶ፣ በአቃቤ ህግ የቀረበባቸው ማስረጃ ግን “የሽብር ተግባርን ለመፈፀም መዘጋጀትን እና መሞከርን” የሚያሳይ ስለሆነ፣ የተከሰሱበት አንቀፅ እንዲሻሻልና መከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ በይኗል፡፡

ሌሎች አራት ተከሳሾች ማለትም፣ ሙራድ ሽኩር፣ ኑር ቱርኪ፣ ሼህ ባህሩ ኡመር እና የሱፍ ጌታቸው ደግሞ፤ በሽብር ተግባር በተለያየ መንገድ ስለመሣተፍ በሚለው አንቀፅ በአቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ማስረጃ እንዲከላከሉ ፍ/ቤቱ በይኗል፡፡ የቀድሞ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የአቶ ጂነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሃቢባ መሃመድን ጨምሮ፣ ሃሠን አሊ፣ ሼህ ሱልጣን ሃጂ፣ ሼህ ጀማል ያሲን፣ ሼህ ጣሂር አብዱልቃድር፣ ሃሠን አቢ ሰኢድ፣ አሊ መኪ፣ ሼክ ሃጂ ኢብራሂም፣ ሼህ አብዱራህማን ኡስማን፣ ዶ/ር ከማል ሃጂ እና ሁለቱ ድርጅቶች በአቃቤ ህግ የቀረበባቸው ማስረጃ ወንጀል መፈፀማቸውን ስለማያስረዳ መከላከል ሣያስፈልጋቸው በነፃ ይሠናበቱ ሲል ፍ/ቤቱ ብይን ሠጥቷል፡፡

ይከላከሉ የተባሉት ተከሳሾች፤ የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን ከጥር 22 ጀምሮ ለ5 ቀናት ያቅርቡ ሲል ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ የሚኒስትሩ የአቶ ጁነዲን ሣዶ ባለቤት ወ/ሮ ሃቢባ መሃመድ ሐምሌ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ከሣውዲ አረቢያ ኤምባሲ የሃይማኖት አታሼ ቢሮ፣ ግምቱ ከሃምሣ እስከ መቶ ሺህ ብር የሚገመት የታሠረ ገንዘብ እና በአረብኛ የተፃፉ መፅሃፍት ይዘው ሲወጡ ተገኙ ተብለው ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ይታወሳል፡፡ ለአንድ አመት ከ5 ወራት ያህልም በማረሚያ ቤት ቆይተዋል፡፡ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን የባለቤታቸውን በቁጥጥር ስር መዋል በተመለከተ በወቅቱ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ “ባለቤቴን ባልተሟላ መረጃ ፖሊስ አስሮብኛል” ሲሉ መቃወማቸው ይታወሣል፡፡

Published in ዜና

“የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” የተሰኘ ማህበር ለመመስረት ጋዜጠኞች እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የመድረኩ ጊዜያዊ መስራች ኮሚቴ አስታወቀ፡፡ ከትላንት በስቲያ በኢትዮጵያ ሆቴል ኮሚቴው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የማህበሩ መቋቋም ዋናው አላማ፤ ጋዜጠኞች በስራቸው ለአደጋ የተጋለጡ እንደመሆናቸው፣ ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ ለመረዳዳት የሚያስችል ተቋምም ሆነ ማህበር ባለመኖሩ፣ እርስ በእርስ ለመተጋገዝና ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በሀገራችን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ቢረጋገጥም፣ የመገናኛ ብዙሀን ሙያ ከመጐልበት ይልቅ እያደር መጫጫቱ እንደሚያሳስበው የገለፀው ጊዜያዊ መስራች ኮሚቴው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሙያው ባለቤት የሆኑት ጋዜጠኞች ለተለያዩ ጥቃቶች ሲጋለጡ መቆየታቸውንና እየተጋለጡም መሆናቸውን ጠቁሞ፤ ከጥቃቶቹም ውስጥ ያለ አግባብ መታሰር፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡ “ጋዜጠኞች ለሌሎች መብት የሚታገሉትን ያህል በራሳቸውና በሙያው ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት አልታደሉም” ያለው ኮሚቴው፤ ከዚህ እውነታ በመነሳት ነፃና ገለልተኛ የሆነ፣ ለጋዜጠኝነት ሙያና ለጋዜጠኞች መብት የሚቆም ማህበር ማቋቋም ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ በመግለጫው አብራርቷል፡፡

በቅርቡ በስራ ባልደረቦቹ ላይ የተመሰረተውን ክስ ለመከታተል ወደ ሀዋሳ ተጉዞ ከባድ የትራፊክ አደጋ የደረሰበት የ“ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ የጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ጉዳይ ለማህበሩ መቋቋም ምክንያት እንደሆነ የገለፀው ኮሚቴው፤ በአደጋው ወቅት ጋዜጠኛውን ለመታደግ፣ ለጋዜጠኝነትና ለጋዜጠኞች የሚቆረቆሩ ተቋማት አለመኖራቸው እንደተረጋገጡ ጠቁሟል፡፡ በጋዜጠኞች ላይ ለሚደርሱ አይነተ ብዙ ችግሮች ፈጥኖ የሚደርስ “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” የተሰኘ ማህበር ለመመስረት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የገለፀው ኮሚቴው፤ ለሙያው ፍቅርና ክብር ያላቸው ጋዜጠኞች በአባልነት እንዲሳተፉ ጥሪ አስተላልፏል።

ኮሚቴው ማህበሩ ከተቋቋመ በኋላ ያከናውናቸዋል ያላቸውን ዋና ዋና ተግባራት ይፋ ያደረገ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 29 መሰረት የተፈቀደውን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ለማስከበር፣ የጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ፣ በተከታታይ ትምህርትና ስልጠና ሙያዊ ብቃት ለማስጠበቅ፣ በጋዜጠኞች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የህግ አገልግሎት ድጋፍ ለማድረግና በዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ጋዜጠኞች እውቅና ለመስጠት የሚሉት ይገኙበታል፡፡ መድረኩ በዋናነት በአባልነት የሚያቅፋቸው በጋዜጠኝነት ሙያ በማንኛውም መገናኛ ብዙሀን መስክ በማገልገል ላይ የሚገኙትን ሲሆን በሙያው ላይ ለመሰማራት በሂደት ላይ የሚገኙትንና ከሙያው ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸውን ግለሰቦች በተባባሪ አባልነት ያስተናግዳልም ተብሏል፡፡ ጋዜጠኞች በምስረታው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና በቅርቡ በሚጠራው ጠቅላላ ጉባኤ በመገኘት የማህበሩ አመራሮች ምርጫ ላይ እንዲሳተፉ ኮሚቴው ጋብዟል፡፡

Published in ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ ሊደርሱ የሚችሉትን እሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን ነዋሪውንና ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ፣ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰተም ፈጥኖ በመቆጣጠርና በማረጋጋት የነዋሪውን ደህንነት (Safety) እንዲጠበቅ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ተልዕኮው መሰረት ህዳር 25 ቀን 2006፣ ከቀኑ 9፡15 ገደማ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ጆንያ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የገበያ ማዕከል የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ፣ የእሳት አደጋው ከተከሰተው በላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ የእለቱን አደጋ አስመልክቶ ጋዜጣችሁ ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 28 ቀን 2006 እትሙ ላይ “ከንቲባ ድሪባ የእሳት ቃጠሎ ተጐጂዎችን አቤቱታ አጣራዋለሁ አሉ” በሚል ርዕስ፣ የተቋማችንን ተልዕኮ በሚያሳንስና ገጽታችንን በሚያበላሽ እንደዚሁም ተቋማችንን ከህዝብ ጋር በሚያጋጭ መልኩ፣ መልካም እይታና ሚዛናዊነት የጐደለው ስሜትን ብቻ ያስተናገደ ዘገባ ማቅረባችሁ መስሪያ ቤታችንን አሳዝኗል፡፡ በዘገባችሁ ላይ አንዳንድ ነጋዴዎች፤ “የእሳት አደጋ ሰራተኞች ከበላይ አካል መመሪያ አልተላለፈልንም በሚል ሰበብ ቆመው ሲያዩ ነበር” ለተባለውኧ በማናቸውም እሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን ምክንያት መተኪያ የሌለውን የሰውን ህይወትና ንብረት ማዳን ሰብአዊ አገልግሎት ጭምር ከመሆኑም ባሻገር፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበት ዋናው አላማ ነው፡፡

ማናቸውንም አደጋ ፈጥኖ ለመቆጣጠር ባለሙያዎችም ሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የመስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎች፤ በአደጋው ስፍራ የሚገኙ በመሆኑና ስራው ላይም በቀጥታ የሚሳተፉበት አሰራር እንጂ የሰው ህይወትና ንብረት ለማዳን የማንም አካል ትዕዛዝ ወይም ፈቃድ ተጠይቆ አያውቅም፤ ወደፊትም አይጠየቅም፡፡ አንዳንድ የመስሪያ ቤታችን ሰራተኞች ጉቦ ጠይቀዋል ለተባለውም፣ እንደዚህ አይነት አሉባልታ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን በግለሰቦች የሚነገር ሲሆን ይህንኑ ለማጣራት በሚደረገው ሂደትም የጋዜጣ ዝግጅት ክፍላችሁን ጨምሮ “ሲሉ ሰማን” ከማለት ውጪ ተጨባጭ መረጃ አልቀረበም፡፡ ይሁን እንጂ ስራችን በህዝብ ፊት የሚሰራ በመሆኑ፣ ተጨባጭ መረጃዎች ካሉ ከህግ አካላት ጋር ተባብረን የምንሰራ መሆኑን ማረጋገጥም እንወዳለን፡፡ ሌላው አደጋዎች ሰፋ ሲሉ ሌሎች ተባባሪ ተቋማትንና የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያጋብዙ በሆነ ጊዜ ሁሉ በትብብር ስንሰራ ቆይተናል፡፡ በዚህ የእሳት አደጋም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ፤ ኤርፖርቶች ድርጅት እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎችና የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ፣ በሁሉም ቅርንጫፍ ጣቢያዎቻችን የሚገኙ የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎችንና አምቡላንሶችን ከበቂ ባለሙያዎች ጋር በማሰማራትና ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ አደጋው የከፋ እንዳይሆን ማድረግ ተችሏል፡፡

ጋዜጣችሁ ባቀረበው ዘገባ ግን የአደጋ መቆጣጠር ሰራተኞቻችንም ጭምር የአደጋው ሰለባ በመሆን አደጋውን ለመቆጣጠር ያደረጉትን ጥረት ለማየት አልፈለገም፡፡ ስለዚህም የላክነውን ይሄን ጽሑፍ በጋዜጣችሁ ላይ በማስተናገድ ላቀረባችሁት ዘገባ ማስተካከያ እርምጃ እንድትወስዱ እያሳሰብን፣ ይህ ሳይሆን ቢቀር የህግ አግባቦችን ለመጠቀም የምንገደድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡ አማኑኤል ረዳ ኃይሉ (ኮ/ር) ም/ዋና ዳይሬክተር ከአዘጋጁ፡- ባለፈው ቅዳሜ የጋዜጣችን ዕትም፤ “ከንቲባ ድሪባ የእሳት ቃጠሎ ተጐጂዎችን አቤቱታ አጣራዋለሁ አሉ” በሚል ርእስ የወጣው ዘገባ፣ ጋዜጠኞቻችን አደጋው በደረሰበት ስፍራ ተገኝተው ተጐጂዎች ለከንቲባው ያቀረቡትን አቤቱታ በመስማት፣ ተጐጂዎችን በማነጋገርና ፎቶግራፍ በማንሳት የተጠናቀረ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ደውለን የሚመለከተውን ኃላፊ በማነጋገር፣ በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ምላሽ አካተን ማውጣታችንን ይታወሳል፡፡

Published in ዜና
  • የፓርቲው አመራሮች በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ሀዘናቸውን ገልፀዋል

የታላቁን የነፃነት ታጋይ የኔልሰን ማንዴላን ህልፈት ተከትሎ፣ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ የሀዘን መግለጫ ፕሮግራም በጽ/ቤቱ ያካሄደ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይም ስለኔልሰን ማንዴላ የነፃነት ትግል፣ ከኢትዮጵያ ጋር ስለነበራቸው ቁርኝትና ከማንዴላ ምን ትምህርት ይወሰድ በሚሉት ዙርያ ንግግር ተደርጓል፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከፕሮግራሙ ቀደም ባሉት ቀናት ደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ በመሄድ፣ በኔልሰን ማንዴላ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን መግለፃቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው ወር በገባ በሶስተኛው ቀን በሽብርተኝነት ወንጀል ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙትን እነ አንዷለም አራጌን እንደሚያስብ የጠቆሙት የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቶ አስራት ጣሴ፤ የኔልሰን ማንዴላን የሀዘን መግለጫ ታህሳስ ሶስት ቀን ያደረገው ማንዴላ በነፃነት ትግል፣ በእነ አንዷለም ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳረፉ መሆናቸውን ለመጠቆም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

“ማንዴላን ደቡብ አፍሪካ ወልዳ ብታሳድገውም ኢትዮጵያ ደግሞ አስተምራና ከሞት አትርፋ ለደቡብ አፍሪካ አበርክታዋለች” ብለዋል-ፀሃፊው፡፡ ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት ላይ እያሉ የደቡብ አፍሪካ ነጭ መሪዎች ለግል ጠባቂው ጉታ ዲንቃ፣ ጉቦ ከፍለው ሊያስገድሏቸው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አስራት፤ ሆኖም ጉታ ዲንቃ ምስጢሩን ለማንዴላ አስተማሪ በመንገራቸው ከሞት መትረፋቸውን ጠቅሰው፣ ይህ ምስጢር ወጥቶ ከሞት ባይተርፉ ኖሮ ኢትዮጵያም፣ አፍሪካም ሆነ ዓለም ማንዴላ ስለሚባል ሰው አያውቅም ነበር ብለዋል፡፡ በ25 አመታቸው አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስን (ANC)ን ተቀላቅለው፣ በ46 ዓመታቸው ለእስር የተዳረጉ የነፃነት ታጋይና የመቻቻል ተምሳሌት ኔልሰን ማንዴላ፤ በሮቢን ደሴት ለ27 ዓመት በእስር ተሰቃይተው ከወጡና አፓርታይድ ከወደቀ በኋላ እ.ኤ.አ በ1994 የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡

ማንዴላ፤ “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን እንዳስተማሩና ያሰሯቸው ሰዎች ላይ የቂም በቀል እርምጃ ከመውሰድ እርቅና መግባባትን በመምረጣቸው አለም በአንድ ድምፅ ተስማምቶ “ተምሳሌት” ብሏቸዋል ያሉት አቶ አስራት፤ ከ1ሺ በላይ ሽልማቶችና የማዕረግ ስሞች፣ 85 የክብር ድግሪዎች፣ የ45 የአለም ከተሞች የክብር ነዋሪነት፣ እንዲሁም ማንዴላ የተወለዱበት የልደት ቀናቸው ጁላይ 18 በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ “የማንዴላ ቀን” ተብሎ ተሰይሞላቸዋል፤ ይህ ሁሉ የተገኘው ለነፃነት በተከፈለ መስዋዕትነት ነው ብለዋል አቶ አስራት ጣሴ፡፡

“እነአንዷለም ሽብርተኞች ተብለው ታስረዋል፤ ግን ሽብርተኞች አይደሉም፤ የነፃነት ትግል ቄስና ደብተራ ናቸው” ያሉት አቶ አስራት፤ ኔልሰን ማንዴላም በእንግሊዞች “አሸባሪ” ተብለው እንደነበር አስታውሰው፤ እነ አንዷለምም በቅርቡ የነፃነት ታጋይነታቸውን አለም እንደሚያውቀው ተናግረዋል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አቶ አበባው መሀሪ ያደረጉት ንግግር ደግሞ በኔልሰን ማንዴላና በአፄ ሚኒልክ ላይ ያተኮረ ሲሆን ልክ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ሁሉ አፄ ምኒልክም በኢትዮጵያ ውስጥ የመቻቻልና የአንድነት መንፈስ እንዲኖር ያበረከቱትን አስተዋፅኦ አስታውሰው፤ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የጥላቻና የጐሪጥ መተያየት ፖለቲካ አውግዘዋል። አቶ አበባው አክለውም፤ በምኒልክ ዘመን መቻቻልና አንድነት በመኖሩ የውጭ ጠላትን ማሸነፍ መቻሉን የገለፁ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ማንዴላ ይቅር ባይነትና መቻቻል ካልመጣ፣ ለአገሪቱም ሆነ ለህዝቧ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና
Page 11 of 16