Saturday, 07 December 2013 13:05

“ወይ ወስኑ፤ ወይ መንኑ!...”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እኔ የምለው…ጥያቄ አለን፣ የቦሌ መንገድ ሲሠራ “ሶሪ ፎር ዘ ኢንኮንቪኒየንስ…” ምናምን የሚል ይቅርታ ቢጤ ነገር አንድ፣ ሁለት ቦታ ተቀምጦ ነበር…ታዲያ ምንሊክ አደባባይ አካባቢ ያልተደረገልን…በዚችም የመደብ ልዩነት አለ ማለት ነው? (ዘንድሮ እኮ ነገርዬው … ከእግር እስከ ራስ እየገረመመ ‘የብቃት ማረጋገጫ’ የሚሰጠንና የሚከለክልን በዝቶብናል፡፡ ያውም በር ላይ ካለው… አለ አይደል… ሥራው ጥበቃ ብቻ ከሆነው የጥበቃ ሠራተኛ ጀምሮ!) ገና ለገና ‘ቦልሼቪክ አብዮት’ ‘ዘ ሎንግ ማርች’ ምናምን አልቆለታል ተብሎ ነው እንዴ…ካለው ‘ጫማ ስር መውደቅ፣’ ከሌለው ከ‘ጫማ ስር ለመርገጥ’ መሞከር የበዛው! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ነገረ ሥራችን ሁሉ…አለ አይደል…‘ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት’ እየሆነብን ተቸግረናል፡፡ የምር…የተያዘው በስርአት አልሠራ ብሏል በሌለ አሻንጉሊት… “እንቁልልጭ!” አይነት ነገር ስንባል አስቸጋሪ ነው፡፡ እናላችሁ…ብዙ አገልግሎቶች፣ ወደፊት መሄዱን ተዉት…ባሉበት መቆየት እንኳን እያቃታቸው ይኸው ‘በመነጫነጭ በዓለም ቀዳሚዋ አገር’ ምናምን ሊያሰኘን ነው! ታዲያላችሁ…ዘንድሮ እዚህ አገር እጅግ በጣም አስቸጋሪ እየሆኑ ከመጡት ነገሮች አንዱ ምን መሰላችሁ…በሞባይል ስልክ መነጋገር ነው፡፡ አሁን እኮ “…ሊያገኟቸው አይችሉም…” “መስመሮች ሁሉ ተይዘዋል…” ምናምን ብቻ ሳይሆን እያወራን በየመሀሉ የሚቋረጥብን ነገር ‘እያሳበደን’ ነው፡፡

እና “እንቁልልጩ” በልክ ሆኖብን ቢያንስ እያወራን አታቋርጡንማ! ስሙኝማ…ዘንድሮ ብዙ ስፍራ ነገሮችን ለማስፈጸም ውሳኔ ሰጪ እያጣን ተቸግረናል፡፡ እናላችሁ… እንደሚባለው ውሳኔ ላይ ፊርማቸውን ለማኖር የሚደፍሩ ‘የሚመለከታቸው’ ሰዎች ቁጥር እያነሰ ነው ተብሏል፡፡ (“የተገልጋዮችን ደብዳቤዎች በጊዜ ሳትፈርምላቸው ቀርተህ አጉላልተሀቸዋል…” ተብሎ… አለ አይደል… ዘጋቢ ፊልም ባይሠራበት እንኳን በአደባባይ የተገሰጸ ሰው ብዙ አላየንማ! እናማ… በየመሥሪያ ቤቱ ውሳኔ አሰጣጥ ነገር ያሳስባል፡፡ ውሳኔ ለሚገባው ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ… “ምን እንደሚመጣ ይታወቃል፣ ልጄ ቅዝምዝምን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ነው…” እየተባለ ማድፈጥ ሥራዎችን እየጎተተ ነው፡፡ ስሙኝማ…የውሳኔ መስጠትን ነገር ካነሳን አይቀር…በእግር ኳስ ዳኞች አንጀታችሁ የቆሰለ ሁሉ ይቺን ስሙኝማ…አንድ እግር ኳስ ተጫዋች ከዚህ ዓለም ይሰናበትና ገሃነም ይወርዳል፡፡ ገሃነም በር ላይም ዲያብሎስ ይቀበለዋል፡፡ ዲያብሎስ፡— ባለፈው ሕይወትህ ምን ስትሠራ ነበር? ተጫዋች፡— እግር ኳስ ተጫዋች ነበርኩ፡፡ ዲያብሎስ፡— ጥሩ፣ እንግዲያው ሰኞ አንድ ጨዋታ ይኖርሀል፡፡ ማክሰኞ ሁለት፣ ረቡዕ አንድ፣ ሐሙስ ሁለት፣ ዓርብ አንድ፣ ቅዳሜና እሁድ ሁለት ግጥሚያዎች ይኖሩሀል፡፡ ተጫዋች፡— በጣም ደስ ይላል፡፡ ምድር ላይም እንዲህ እንደ ልቤ ለመጫወት ዕድል ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ዲያብሎስ ይመጣና “ጌታው፤ ስህተት ተሠርቷል፡፡

መግባት የነበረብህ መንግሥተ ሰማያት ነበር፣” ይለዋል፡፡ ከዛም ተጫዋቹ ወደ መንግሥተ ሰማያት ይሄድና ቅዱስ ዼጥሮስን በር ላይ ያገኘዋል፡፡ ቅዱስ ዼጥሮስ፡— ባለፈው ሕይወትህ ምን ስትሠራ ነበር? ተጫዋች፡— እግር ኳስ ተጫዋች ነበርኩ፡፡ ዲያብሎስ፡— እንግዲያው የመጀመሪያ ጨዋታህን ከስድስት ወራት በኋላ ታደርጋለህ፡፡ ተጫዋች፡— ስድስት ወር! ገሃነም ሳለሁ በየቀኑ አንድ ጨዋታ ነበረኝ፣ አንዳንድ ቀን እንደውም በቀን ሁለት ጨዋታዎች ነበሩኝ፡፡ እዚህ ችግሩ ምንድነው፣ በቂ ተጨዋቾች የሉም እንዴ? ቅዱስ ዼጥሮስ፡— ተጨዋቾች እንኳን ብዙ አሉን፣ ችግሩ ዳኞቹ በሙሉ ገሃነም መሆናቸው ነው፡፡ ይሄ የምር ቂ…ቂ…ቂ… ያሰኛል፡፡ ለካስ “ዳኛ በድሎን ነው…” ምናምን የሚባለው ነገር…አለ አይደል…ዳኞቹ “ገሀነም መግባቴ ካልቀረ…” እያሉ ነው ፍጹም ቅጣት ምት የሚከለክሉን! ከኳስ ሳንወጣ…ይቺን ቀልድ አንብቡልኝማ…አንድ ምሽት ሜሲ የሆነ ፓርቲ ላይ አንዲት ቆንጅዬ ልጅ ያገኛኝና ይግባባታል፡፡ ከዛማ… በቃ፣ ‘እነሆ በረከት’ ሊባባሉ ይስማማሉ፡፡ እሷዬዋ ሜሲን ቤቷ ይዛው ትሄድና “ጋደም ብለህ እየተዘገጃጀህ ጠብቀኝ” ብላ መታጠቢያ ቤት ትገባለች፡፡ ትንሽ ቆይታ ስትመለስ ከሜሲ ጎን ዣቪና ኢኒዬሰታ መለመላቸውን ተኝተው ታይና ትደነግጣለች፡፡ ፊቷን ኩስትርትር አድርጋም “ምንድው ይሄ፣ ምን እየተካሄደ ነው?” ትላለች፡፡

ሜሲ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ያለ ሁለቱ እርዳታ ብቻዬን ጎል ማግባት አልችልማ!” ‘እዛ’ጋም’ “ጎል!” ይባላል እንዴ!” ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ፣ ጎል የሚባልም ካለ እኮ ኦፍ ሳይድ ምናምን የሚሏቸውም ህጎች ይሠራሉ፤ አሁን ካልጠፋ ህግ ኦፍ ሳይድን ምሳሌ የምታደርገው ምን ለማለት ነው…ለምትሉ ወዳጆቼ… “ኖ ኮሜንት!” ልጄ፤ ዘንድሮ…‘ኖ ኮሜንት’ን የመሰለች የብረት አጥር የለችም፡፡ እናላችሁ…ውሳኔ ሰጪዎች ሁሉ ‘ገሃነም ገብተው’ ካልሆነ በስተቀር… ‘እንቁልልጩ’ ይቅርብንና ውሳኔ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ውሳኔዎች ይሰጡንማ! ስሙኝማ…ነገሬ ካላችሁ “ከእንዲህ ዓመት በኋላ እንዲህ እናደርጋለን…” “በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ አይነት ለውጦች እናመጣለን” ማለት አሪፍ ማምለጫ የሆነ ይመስላል፡ አሀ…“ለውጥ እናመጣለን…” ምናምን ማለት ‘ልማታዊ’ ነዋ! ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ስለ አምስትና አሥር ዓመት ዕቅድ ቅብጥርስዮ ሲያወሩ “ምነው እስከዛሬ ያለችዋን ሚጢጢዋን ሥራ ማሳካት አቃታችሁ!” ብሎ የሚጠይቅ መጥፋቱ! እና የምለው…እዚህ አገር ‘ቦተሊካዊ’ ስርአታችን…ለእኛ ለሰፊዎቹ ህዝቦች በሚገባን መልኩ ይገለጽልንማ! ምክንያቱም በየጊዜው የሚለዋወጡት ነገሮች…በአራድኛው ‘ጦጣ’ እያደረጉን ነው፡፡ “ይሄ መመሪያ የካፒታሊስት ምናምን ይመስላል…” ብለን ሳንጨርስ ሌላ መመሪያ ይተካል፡፡ “ይሄኛው ደግሞ ከኮሚኒስት ማኒፌስቶ ቃለ በቃል የተወሰደ ይመስላል…” እንላለን፡፡ ስሙኝማ…እግረ መንገዴን፣ ይቺን አሪፍ ነገር እዩዋትማ…የተለያዩ ፖለቲካዊ ስርአቶች ገለጻ ነገር ነች፡፡ ሶሻሊዝም፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ መንግሥት አንዱን ይወስድብህና ለሌላ ሰው ይሰጠዋል፡፡ ኮሚኒዝም፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ መንግሥት ሁለቱንም ይወስድብህና ወተቱን ይሰጥሀል፡፡ ፋሺዝም፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ መንግሥት ሁለቱንም ይወስድብህና ወተቱን ይሸጥልሀል፡፡ ወታደራዊ ጁንታ፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ መንግሥት ሁለቱንም ይወስድብህና አንተን ደግሞ ይረሽንሀል፡፡ ቢሮክራሲ፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ መንግሥት ሁለቱንም ይወስድብህና በስህተት አንዷን ገድሎ ወተቱን ፍሳሽ ማስወገጃ ውስጥ ይደፋዋል፡፡

ካፒታሊዝም፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ አንዱን ትሸጥና ኮርማ ትገዛለህ፡፡ ያልተበረዘ ዲሞክራሲ፡— ሁለት ላሞች አሉህ። ወተቱ ለማን መድረስ እንዳለበት ጎረቤቶችህ ይወስናሉ፡፡ የውክልና ዲሞከራሲ፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ ወተቱ ለማን መድረስ እንዳለበት የሚወስነውን ሰው ጎረቤቶችህ ይመርጡልሀል፡፡ የአሜሪካ ዲሞክራሲ፡— መንግሥት ለእሱ ድምጽ ከሰጠህ ሁለት ላሞች ሊሰጥህ ቃል ይገባልሀል፡፡ ከምርጫው በኋላ መንግሥት በሠራው ሸፍጥ ምክንያት ከስልጣን ይወገዳል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ጉዳዩን የ“ካውጌት” ቅሌት ብለው ይሰይሙታል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት፡— ሁለት ላሞች አሉህ፡፡ ወይ ወተቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ትሸጣለህ፣ አለበለዛ ጎረቤቶችህ ይገድሉህና ላሞቹን ይወስዳሉ፡፡ እናማ…ስታስቡት ከአብዛኞቹ ነገሮች ጥቂት፣ ጥቂት ያለን አይመስላችሁም! ለሁሉም መጀመሪያ ግን የ‘ሁለቱ ላሞች’ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለት ላሞች ለሌሉት ገለጻው አይሠራማ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ስሙኝማ…ዛሬ መቼም ተረት በተረት ሆነናል…አሁንም ስለ እግር ኳስ ዳኞች ስሙኝማ፡፡ ዓለም ካለቀች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በመንግሥተ ሰማያትና በገሃነም መካከል የድንበር ጭቅጭቅ ይነሳል፡፡ የመንግሥተ ሰማያት ተወካዩ መልአክ ለጉዳዩ በቶሎ መፍትሄ ለመፈለግ ዲያብሎስን ለድርድር ይጋብዘዋል፡፡ ዲያብሎስም ጉዳዩን ለመፍታት በመንግሥተ ሰማያትና በገሃነም መካከል የእግር ኳስ ግጥሚያ እንዲካሄድ ሀሳብ ያቀርባል፡፡ መልአኩም ፍትሀዊ በመሆኑ ለዲያብሎስ እንዲህ ይለዋል፡ “ሙቀቱ ጭንቅሌህን አዛብቶታል መሰለኝ። ጨዋታው የአንድ ወገን ብቻ ነው የሚሆነው፣ ምርጦቹ ተጫዋቾች በሙሉ መንግሥተ ሰማያት እንደሆኑ ታውቃለህ፡፡” ዲያብሎስ ሳቅ ብሎ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ልክ ነህ፣ ግን ዳኞቹ በሙሉ እኛ ዘንድ ናቸው፡፡

” ስሙኝማ…ዲያብሎስን ልንጠይቀው የምንፈልገው ነገር አለ…እባክህ ውሳኔ ሰጪዎች ሁሉ አንተ ዘንድ ሊመጡ ‘ዌይቲንግ ሊስት’ ላይ ካሉ ሰርዝልንማ! አሀ…እዛ መሄዳችን ካልቀረ ለምን ብለን ነው ደግ ሥራ የምንሠራው እያሉ መከራችንን እያበሉን ነው፤ ወይም ለባሰባቸው እዛው ገሀነም ውስጥ…አለ አይደል…‘ጨለማ ቤት’ ነገር አዘጋጅልንማ! አሀ… እሱን እንኳን ፈርተው ጉዳያችንን ሊፈጽሙልን ይቻላሉዋ! እናላችሁ…ብዙ ነገር እየተበላሸ ያለው ‘አስፈራሚ’ “አቤት” ሲል ‘ፈራሚ’’ አልሰማሁም እያለ ነው፤ ስሙኝማ…ዘንድሮ ያለምንም ‘ደጅ መጥናት’ የሚፈረም ነገር… የተጫዋቾች የዝውውር ሰነድ ብቻ ይመስላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እናላችሁ…ሰዉ ሲከፋው አንድዬን “ወይ ውረድ፣ ወይ ፍረድ!” እንደሚለው ሁሉ…አለ አይደል… ጉዳዩን የሚፈጽሙለት ‘ከባድ ሚዛኖች’ እያጣ…አለ አይደል… “ወይ ወስኑ፣ ወይ መንኑ!” ማለት ደረጃ እንዳይደርስ ልብ ያለው ልብ ይበልማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Saturday, 07 December 2013 13:03

የፀጉር አስተካካዩ ኑዛዜ

(በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ አጭር ልብወለድ)

ሰዎች ሲያቆላምጡት “ገብሬ” ይሉታል፤ ሙሉ ስሙ ግን ገብረሚካኤል ነው፡፡ በሰፈራችን ነዋሪነቱ ለብዙ ጊዜ ይታወቃል። ዝምተኛ፣ ለአለባበሱ እምብዛም ትኩረት የማይሰጥና ብዙ ጊዜ ለብቻው መሄድ ብቻ ሳይሆን ማውራትም የሚወድ ነበር፡፡ አንድ ጥዋት የዕድራችን ጥሩንባ ነፊ ከየተኛንበት በጥሩንባው ድምጽ ቀሰቀሰና የገብሬን ድንገተኛ ሞት አረዳን፡፡ ገብሬ ሞቶ የተገኘው በኪራይ በሚኖርባት አንድ ክፍል ውስጥ ራሱን ሰቅሎ ነው፤ አልጋው ላይ የሞቱን ምክንያት የምታስረዳ አንዲት ገጽ ወረቀት ተገኝታለች፡፡ “ይድረስ ለሚመለከታችሁ ሁሉ! ግን የእኔ ጉዳይ ማንን ይመለከታል? ኤልሲን? መንግሥትን? ግለሰቦችን? ቀበሌውን? ወይስ እግዜርን? ሁሉም አይመለከታቸውም፡፡ የሚመለከታቸው ቢሆኑማ ይህን ያህል ዘመን የመከራ ዶፍ ሲወርድብኝ አንዳቸው እንኳ “አይዞህ” ይሉኝ ነበር፡፡ እንዲያውም እኔ በችጋር አለንጋ በተገረፍሁ ቁጥር ከጐኔ ሆነው ከማበረታታት ይልቅ ቁስሌ ይበልጥ እንዲያመረቅዝ በስንጥር ይወጉኝ ነበር፡፡

የሆነ ሆኖ ቢመለከታቸውም ባይመለከታቸውም ፍጻሜዬን ግን ሊያውቁ ይገባል፤ ለዚህ አይደል ይችኑ የኑዛዜ ጽሑፍ ማስፈሬ፡፡ ኤልሲንና ውሽማዋን ያሉት ሞቴ ሊያስደስታቸው ይችል ይሆናል፡፡ ምን ቸገረኝ? ቢፈልጉ ዲጄ ቀጥረው የብሔር ብሔረሰቦችን ዘፈን እያስዘፈኑ ይጨፍሩ፤ ልብ ካላቸውም ለዛሬዋ ዕለት እንኳ ትንሽ ይዘኑልኝ፡፡ ግን ከዛሬ በኋላ ቢያዝኑልኝስ ምን ይፈይድልኛል? ለነገሩ ደብዳቤ የምጽፈውም ዝም ብዬ ነው፤ እኔን ሰው ብሎ ማን ያነብልኛል? አይ መነበብስ ይነበብ ይሆናል፤ የእኛ አገር ሰው በቁም እርዳ አይበሉት እንጂ ወሬ ማዳነቅማ ማን ብሎት? የቤት ሠራተኞችን ለዘበኛና ለመንደር አውደልዳይ ሲያቃጥሩ የሚውሉት ኤፍ ኤሞችስ ለዚህማ ማን ይቀድማቸዋል? ወሬውን እየተቀባበሉ ያራግቡትና ቢያንስ ከንፈራቸውን የሚመጡልኝ “ደጐች” ይኖሩ ይሆናል፡፡ ታሪኬን በአጭሩ መጻፍ ቢጠቅመኝም ባይጠቅመኝም ቢያንስ በዚህ እድሜዬ ለምን ሞቴን እንደመረጥሁ፣ ማንም እንዳልገደለኝ፣ ግን ቤት ያከራዩኝ ሰዎች በተለይ ጋሼ ዋለልኝ በሞቴ ተጠርጥረው አንድ ሌት እንኳ በፖሊስ ጣቢያ እንዳያድሩ ስል ይችን ኑዛዜ መጻፍ ግድ ሆኖብኛል፡፡

እናቴ ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ ነበር የምትኖረው፡፡ አባቴን ግን እንኳን እኔ እስዋም አታውቀውም፡፡ የተረገዝሁት ከአንድ ማንነቱ ከማይታወቅ እረኛ መሆኑን ነግራኛለች፡፡ እናቴ የምትተዳደረው ኩበት ለቅማ፣ እሱኑ ተሸክማ መንደር ለመንደር እየዞረች በመሸጥ ነበር፤ በአንድ ጐደሎ ቀን እንደልማዷ ኩበት ለቀማ መስክ ወርዳ ሳለ፣ ድንገት መዕላከ ሞት የመሰለ እረኛ ተከመረባትና ተረገዝሁ፤ እኔን ለማሳደግ ያላየችው የመከራ አይነት የለም፡፡ ራስዋን እየቀጣች እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ብታስተምረኝም ሊያስቀጥለኝ የሚችል ውጤት አልመጣልኝም፡፡ በመሆኑም ከህጻንነቴ ጀምሬ እሰራው የነበረውን የአገናኝነት ሥራ አጠንክሬ ቀጠልሁበት፡፡ በዚህ ሥራ የማይናቅ ብር አገኝ ነበር። የተሻለ ብር የሚያስገኝልኝ ግን ባለትዳር ሴቶችን አሳምኜ ከሚፈልጓቸው ወንዶች ጋር ሳገናኝ ነበር። ምክንያቱም ባለትዳር ሴቶች እንደ ተማሪዎችና ሴት የመንግሥት ሠራተኞች በቀላሉ አይገኙም፡፡ ቢገኙም ሆቴል መግባት ስለማይችሉ የሚገናኙበትን ቦታ ማዘጋጀትም የእኔ ኃላፊነት ሰለነበር ሥራው አስቸጋሪ ነው፡፡ ደብረ ብርሃን ጠባብ ከተማ በመሆኗ እንኳንስ እንዲህ ላለው ጥብቅ ምሥጢር ለሌላውም ቢሆን አስቸጋሪ ናት፡፡

ስለዚህ ተፈላላጊዎችን የማገናቸው ዘመድ ቤት፣ ወይም ጠበል የሄዱ በማስመሰል ጫካ ውስጥ ነበር፡፡ ዘመድ የሚባለው ብር ተከፍሎት አልጋውን የሚያከራይ ሁነኛ ሰው ወይም ከጓደኞቼ የአንዱ ቤት ሲሆን ሰዋራ ቦታ ሁሉ ብዙ ሥራዎች ተሰርተውበታል፡፡ እነሱ ዓለማቸውን ሲቀጩ ውስጤ በፍትወት እየነደደ የጥበቃ ሥራ ሁሉ አከናውን ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ የአንዱ ዶክተር ሚስት “ወደ ጉር ገብርኤል ጠበል ሄድሁ” ብላ ካዘጋጀሁላት ሰዋራ ቦታ ከሚፈልጋት አንድ ባለ ትዳር ጋር ዓለሟን ስትቀጭ፣ ዶክተሩ ባሏ ለካ ይከታተላት ኖሮ ያረጁ መነኩሴ መስሎና ራሱን በልብስ ለውጦ ከች አለ። ወዲያው አንድ ጥይት ተኮሰና ታፋዬን መታኝ፤ ሚስቱና ውሸማዋ ተኩሱን ሰምተው ከወደቁበት ሲነሱ የተቀባበለ ሽጉጥ ተደግኖባቸው አዩ፡፡ ሚስቱን በሁለት ጥይት ደረቷን ከሰነጠቀ በኋላ፣ ውሽምየው ሱሪውን ሳይታጠቅ ሬሳዋን ተሸክሞ ወደፊት እንዲሄድ ዶክተሩ አዘዘው፤ ውሽምዬው በሃፍረትና በድንጋጤ ክው እንዳለ የታዘዘውን መፈፀም ግዴታው ነበር፡፡ ወደፊት በሄደ ቁጥር ወደ አደገኛው የአሞራ ገደል እየተጠጋ መሆኑን በፍጹም ልብ ያለ አይመስልም፡፡ አሞራ ገደል ጫፉ ላይ ሲደርስ የተሸከመውን አስከሬን ቁልቁል እንዲወረውረው በዶክተሩ ታዘዘና ያለ አንዳች ማቅማማት ፈጸመው። ቀጠለና “ወደኔ ዙር!” የሚል ትዛዝ ሰጠው፤ ውሽምየው በፍርሃት እየራደ ወደ ዶክተሩ ዞረና መሬት መሬቱን ያይ ጀመር፡፡

ወዲያው ራቁት የነበረ ብልቱን በጥይት መታውና ተንገዳገደ፤ በሁለተኛው ጥይት ግንባሩን ሲፈልጠው ወደ ዶክተሩ ክንብል አለ፤ አስከሬኑን የሚስቱ ሬሳ ወደተጣለበት ገደል ወረወረና ይፎክር ጀመር፡፡ ቀጣዩ አስከሬን እኔ እንደምሆን ስለተረዳሁ እንደምንም ተንፏቅቄ ቦታ ቀየርሁ፤ የተመታ እግሬን አንገቴ ላይ በነበረው ፎጣ ግጥም አርጌ አሰርሁና የደሙን ነጠብጣብ ተከትሎ እንዳይመጣ አፈር አለበስሁት፡፡ ግን በደንብ ቢፈልገኝ ብዙም ስላልራቅሁ በቀላሉ ሊያገኘኝ ይችል ነበር፤ ሆኖም እኔን በመፈለግ ፈንታ ሲያቅራራና ሲፎክር ቆይቶ ያቀባበላቸው ጥይቶች እስከሚያልቁ ድረስ ወደ ሰማይ ከተኮሰ በኋላ ሚስቱና ውሽማዋ ወደ ወደቁበት ገደል ራሱን ወረወረ፡፡ አለመሞቴ ቢያስደስተኝም ለሶስት ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኔ አሳዘነኝ፡፡ እንደምንም እየተንፏቀቅሁ አንድ ለጋ ባህር ዛፍ ዘነጠልሁና እሱን ምርኩዝ በማድረግ ወደ መኪና መንገድ አመራሁ፤ እግዜርም እንደ ሰው ጨካኝ አለመሆኑን ያወቅሁት ያንለት ነው፡፡ ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች እንዲያሳፍሩኝ ብማጠናቸውም በጄ የሚሉኝ እንዳንጣሁ ሁሉ አንድ የቤት መኪና የሚያሽከረክሩ አዛውንት ግን ሳልጠይቃቸው አጠገቤ መጥተው መኪናቸውን አቆሙ፡፡ በመንገድ ላይ ማንነቴን ደብቄ፣ እግሬን የተጐዳሁትም በዱርዬ ተደብድቤ መሆኑን እየነገርኋቸው አዲስ አበባ ገባን፡፡ አዲስ አበባን ደሞ ከወሬ በቀር አላውቃትም፤ ግን በመኪናቸው ላመጡኝ አዛውንት አውቶብስ ተራ አካባቢ ዘመድ እንዳለኝ ዋሽቼ ነግሬያቸዋለሁ፡፡

አዲስ አበባ ስደርስ ግራው ገባኝ፤ ረጋ ብሎ መሄድ የሚያስቀጣ ይመስል መኪናውም ሰውም ይጣደፋል፡፡ ለተወሰኑ ቀናት መንገድ ላይ እያደርሁ በበረንዳ አዳሪዎች ስታገዝ ቆየሁ፤ ቁስሌ ቢድንም እንደ ቀድሞ መሮጥ የማይታሰብ ሆነ፡፡ ስለዚህ ጓደኞቼ “ሸንኮ” የሚል ቅጽል አወጡልኝ፡፡ “ሸንካላ” ማለታቸው ነው፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ “ጋሼ አበራ” የሚባሉ ደግ ሰው ሁልጊዜ ጥዋት ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር ከሱቃቸው በረንዳ ላይ መደዳውን ተኝተን ያዩናል፤ እኔን በሸንካላነቴ ምክንያት ያዝኑልኝ ስለነበር ለአንድ የወንዶች ውበት ማሰልጠኛ ብር ከፍለው እንድማር አደረጉ፡፡ በትምህርት አቀባበሌ የተሻልሁ ስለነበርሁ፣ ስልጠናውን እንደጨረስሁ ማሰልጠኛው በመምህርነት ቀጠረኝና ደሞዝ ማግኘት ቻልሁ፡፡ ትንሽ ገንዘብ አጠረቃቅሜ ምስኪን እናቴን ለመርዳት ሳጠያይቅ በድንገት ስለጠፋሁባት እኔኑ ፍለጋ በየቦታው ስትንከራተት ቆይታ፣ በሃዘንና በችጋር ባዶ ቤት ውስጥ ሞታ መገኘቷን ሰማሁ። ራሴን መቆጣጠር ባለመቻሌ በሽተኛ ሆንሁና ለእናቴ ያጠራቀምሁትን ገንዘብ ለህክምና ተቋማት መገበር ግድ ሆነብኝ፡፡ ሥራዬን በተገቢው መንገድ ማከናወን ባለመቻሌም ከውበት ማሰልጠኛው ተባረርሁ። ግን ከአንድ ፀጉር ቤት ተቀጠርሁና መሥራት ጀመርሁ፤ ሆኖም የተደራረቡ ችግሮች ገጠሙኝ። አንደኛ የአንዳንዱ ሰው ፎረፎር አመድ ላይ ተንከባልላ የተነሳች አህያ ይመስል ለማበጠር ትንሽ ስነካው በአፍ በአፍንጫዬ ግጥም ይልና መተንፈስ እስከሚያቅተኝ ድረስ ጤናዬን ያውከዋል፡፡ ሁለተኛ የፀጉሩ ብናኝ ሳንባዬን እየዘጋ እቸገር ጀመር፤ ከሁሉም ችግር የሆነኝ ግን የኤልሲ ጉዳይ ነው፡፡ ኤልሲ ሴተኛ አደራ ብትሆንም በጣም የምወዳት ልጅ ናት፡፡ “የሴተኛ አዳሪነት ህይወት ሰልችቶኛል እንጋባ” ብላ አብረን እየኖርን ሁሉ ትባልግ ነበር፡፡ ከልቤ ስለምወዳት ብቻ እንደማላውቅ ሆኜ አብሬያት ለመኖር ተገደድኩ፡፡

ከእሷ ውጭ ዘመድ የለኝማ! አንድ ቀን ግን መረረኝ፤ ሥራ ላይ ስላመመኝ በጊዜ ነበር ወደ ቤቴ ያመራሁት፡፡ ያችን ምስኪን መዝጊያ እንደ ልማዴ ገፋ አድርጌ ስገባ ኤልሲ ከምኖርበት ቤት ዘበኛ ጋር ክርና መርፌ ሆነው አገኘኋቸው፡፡ ከመደንገጤ የተነሳ እንደ ተወጋ አጋዘን ጓጉሬ ወደቅሁ፡፡ ስነቃ ኤልሲ የለችም፤ ዘበኛው ግን በእሱ ብሶ የጐሪጥ ሲያየኝ ነደደኝ፡፡ የት እንደ ሄደች ልጠይቀው አማረኛና ቅናት አፌን ለጐመው፡፡ ትመጣለች ብዬ ብጠብቃትም በዚያው የውሃ ሽታ ሆነች፡፡ በእጅ ስልኳ ደወልሁለት፤ መጀመሪያ አላነሳችውም፡፡ በሁለተኛው ግን አነሳችና እንደ ዋልጌ ዝንጀሮ አስካካችብኝ፤ ቀጥላም “ዘቡሌውን አየኸው አይደል እንዴት እንደሚሠራ ሸንኮ” ብላ ስልኩን ጠረቀመችው፡፡ ከድርጊቷ ይልቅ ሳቋ ሲያናድድ አይጣል ነው፡፡ ደሞስ “ዘቡሌው እንዴት እንደሚሠራ አየኸው አይደል” ያለችኝ ምን ማለት ፈልጋ ነው? እስከዚያን ቀን ድረስ በወንድነቴ ትኮራና ትደሰትበትም እንደነበር ራሷ በአንደበቷ ነግራኛለች፡፡ ቢሆንም የእጄን ያገኘሁ ያህል ይሰማኛል፤ የሶስት ሰዎች ህይወት በአንድ ቀን እንደ አበባ የተቀጠፈው በእኔ ምክንያት አይደል? ግን ሳላስቀይማት ለምን ታስቀይመኛለች? ሸሌ መሆኗን እያወቅሁ ነው ያገባኋት፡፡ በኤልሲ ድርጊት እየተበሳጨሁ መሥራት ሁሉ ተሳነኝ፡፡

ዘበኛውም በወጣሁ በገባሁ ቁጥር ይገላምጠኛል፤ ብቻዬን ስሆንም አንድ ቀን እንደ ዶሮ አንገቴን ጠምዝዞ ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ እንደሚጨምረኝ ይዝትብኛል፡፡ ከዚህ ይባስ ብለው ትናንት እሱና ኤልሲ በእሷ ስልክ ደወሉልኝና ከአንድ ቤርጐ ውስጥ ዓለማቸውን እየቀጩ መሆናቸውን አረዱኝ፡፡ ሲሳሳሙ ሁሉ በስልክ ያሰሙኝ ነበር፡፡ ቢችሉ ሁለቱም መለመላቸውን ሆነው የሚሠሩትን ቢያሳዩኝ ደስ እንደሚላቸው አፍ አውጥተው ነገሩኝ፡፡ ትላንት የተሰማኝን ስሜት እንዴት መግለጽ እችላለሁ? ሌቱን ሙሉ ሳነባ አደርሁ፡፡ እንባዬ ደግሞ ከዓይኔ ብቻ የሚወርደው አይደለም፤ ልቤ ራሱ ደም ሲያነባ እንዳደረ ይሰማኛል፡፡ እና እንግዲህ ማን ቀረኝ? ምንስ የሚያጓጓኝ ነገር አለ? ለካ ዶክተሩ ሚስቱንና ውሽማዋን ከገደላቸው በኋላ ራሱን በኩራት ወደ ገደል የወረወረው ወዶ አልነበረም፡፡ ስለዚህ እኔም በቃኝ፤ ተሸነፍሁ፡፡ ምንም ድሃ ብሆን፤ አለኝ የምለው አንድ ሰው በምድር ላይ ባይኖረኝም ይች የብር ከሃምሳ የሲባጐ ገመድ በመጨረሻዋ ቀኔ አብራኝ ናትና አመስግኑልኝ፡፡

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 07 December 2013 13:01

እንኳን ለዓመት ጉድ አበቃን!

ዘንድሮም ልክ በዓመቱ፣ እንደአምናና እንደ ሃቻምና
የሐምሌ ጐርፍ ሞላና፣ ይኸው ለዓመት ጉድ
በቃና …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፣ …
ዝግጁው ማዘጋጃ ቤት፣ ዜና መግለጫ ለማውጋት
እንደጥምቀተ ባሕር ወግ፣ የዓመቱን ጐርፍ ለማውሣት
ደረሰ ፍል ውሃ ሜዳ፣ በጋዜጦች አጀብ ብዛት
ለዓመቱ ዜና ገብ ቂጥ፣ “ካሜራ ማን ዙም-ኢን ዙም አውት”
ዘንድሮ ለማወዳደር፣ ከሀቻምናው የዝናብ መዓት
የዓመቱን ፋንፋር ለሕዝቡ፣ በቴሌቪዥን ለመንፋት! …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፤
እኛም ለዓመት ጉድ በቃና፤ …
ከተማው በዶፍ ታጠበ፣ ዝናብ ሳይሆን መዓት ጣለ
ዘቀጠ ተብከለከለ
ቤት ንብረት ተግበሰበሰ፣ ገደል መቀመቅ ተጣለ
መኪናው እንደ አሻንጉሊት፣ ከምድር በላይ ተንጣለለ
ተዋጠ ተጥለቀለቀ፣ ጣራና ፎቅ ግቻ አከለ
ወረደ መዓት ወረደ
ሰማይ ቁልቁል ተቀደደ
እንደ ኦሪት ውሃ ጥፋት፣ አራዳ በማጥ ተናደ
የቤት እንስሳው ንብረቱ፣ ስንቱ አስከሬን ተወሰደ
ከእንጦጦ ፍልውሃ ሜዳ፣ ቄራ እንጦሮጦስ ወረደ
አጠበው ምድሩን ጠረገው፣ ዛፍ ግንዱን እየማገደ
ፎቁን ተሸክሞት ሄደ! …
አቤት ጉድ እየተባለ፣ እንዲያው ብቻ በደፈና
አዲስ አበባ ያለ ዕቅድ፣ ከዓመት ዓመት በጥገና
የዘለቄታ መፍትሔው፣ በአስተማማኝ ሳይጠና
በማዘጋጃ ቤት ዲስኩር፣ የተናደው ፎቅ ላይ ቀና
ለአዲስ ጥናት በአዲስ እቅድ፣ላይ ነን እኮ እየተባለ
ጋዜጣም ምሱን ሸለለ
ቴሌቪዥን ተቀበለ
ሬዲዮም ተንበለበለ
ዘንድሮም ልክ በዓመቱ፣ አዲሳባ ጉድ ተባለ!
ዝነኛው የአቃቂ ውሃም፣ ከጊንፊሌ ጋር ፏለለ
ስንቱን ሰው በልቶ ቤት ነዶ
ለዓመት ምሱ ሕዝቡን ማግዶ
እንደ ቅድመ ታሪክ ዘንዶ
ደሞ ለዓመት ያብቃን ብሎ፣ ተንጐማሎ እየኮራ
እየተወሳለተ ዝናው፣ በጋዜጣ በካሜራ
እያስገመገመ ሄደ፣ እንደሞላ እንደ ተፈራ! …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፤
እኛም ለዓመት ጉድ በቃና፤ …
ዝግጁው ማዘጋጃ ቤት፣ ዜና መግለጫ ለማውጋት
ደረሰ ላጋር ቁልቁለት፣ በጋዜጦች አጀብ ብዛት፣
ካሜራ ማን ዙም-ኢን ዙም አውት! ራዲዮ ማይክሮፎንክን አጉላ
ፊንፊኔም ጥማድ ቀበና አቃቂም ድምር ቡልቡላ
የዓመት መዓቱን ወረደ ሞላ ፈላ ሰው ተበላ!
የቀበሌ አዋጅ እምቢልታ
የእሳት አደጋ ኡኡታ
አስከሬን ጠፋ ዕድር ውጡ፣ ዋይታ ጡሩምባ ቱልቱላ
የእግዜር ቁጣ የእግዜር ዱላ! …
እንደ አምልኮ ጣኦት ልማድ፣ እንደ ባሕሎች አሸክላ
ለአዲሳባ ውሃ ግብር፣ የሰው ልጅ እየተቀላ
ክረምት በመጣ ቁጥር፣ ዓማን ዘራፍ ይባላላ! …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፤
እንኳን ለዓመት ጉድ በቃና!
ጸጋዬ ገብረ መድኅን

 

Published in የግጥም ጥግ

ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ “ንግስ” በሚል ርዕስ በብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ ለእይታ ያቀረባቸው ስዕሎች ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ፤ ባለፈው ዐርብ ህዳር 20 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በኤግዚቢሽኑ ስላቀረባቸው ስዕሎችና በአሰራር ላይ ስለሚከተለው መንገድ ሰዓሊው በሰጠው ማብራሪያ ነበር ፕሮግራሙ የተጀመረው፡፡ “ንግስ” በሚል ርዕስ ለእይታ የቀረቡትን ስዕሎች የሰራኋቸው ከሕይወት ልምድ፣ ከንባብ፣ ከታሪክና ከሰማኋቸው ነገሮች በመነሳት ነው ያለው ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤ ሥራዎቹ ተሰርተው ለእይታ እንዲበቁ የሚያስተምርበት ዩኒቨርስቲ ለጥናትና ምርምር ጊዜ በመፍቀድ፤ ልጁ ጋብዛው ወደ ውጭ አገር በሄደበት አጋጣሚ በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች ያያቸው ስዕሎችና የሥነ ጥበብ ታሪክ ተመራማሪው አቶ እሰዬ ገ/መድህን ያደረጉለት ትብብር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልፆ አመስግኗል፡፡ በመቀጠልም ሙያዊ የሆኑ ጉዳዮች ማብራራት ጀመረ፡፡ በማንኛውም ሙያ ውስጥ ተፈጥሮን የሚቃረኑ ሃሳቦች ተግባራዊ ሲሆኑ ይታያል፡፡ ተፈጥሮን መቀየር ስለማይቻል ለምን የበለጠ አናጐላውም የሚል እምነት አለኝ፡፡

በቀለም ቅብ ሥራ ውስጥ “አግዛፊዎች” አሉ፡፡ እነዚህ ከነበሩ ላይ ተነስተው ጉዳዩን ለማጉላት የሚጥሩ ናቸው፡፡ በተቃራኒው “ገዳፊዎች” አሉ፡፡ እነዚህ ቀለም ቅብ ሞቷል እንዲባል ምክንያት ይሆናሉ፡፡ የእኔ አስተሳሰብ የሚመነጨው ከዚህ መነሻ ነው፡፡ ስዕል የምስለው ከተፈጥሮ ጋር ያለኝን መስተጋብር ተመርኩዤ ሲሆን የቀለም ቅብ ሥራ ከባህላዊ አሰራር ተነስቶ “አግዛፊዎች” ዘመን ላይ መድረሱን አምናለሁ፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በሌሎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩና በቀለም ቅብ ሥራ ላይ ለውጥ ያመጡ ሰዓሊያን ነበሩ፡፡ ቀለም ቅብ ሁለት አውታረ መጠን ነው የሚሉ አሉ፡፡ በሦስት አውታረ መጠን መጠቀም ከባድ መሆኑን የሚልጹም አሉ፡፡ አንድ ነገር በማነሱ ምክንያት ሁለት ወይም ሦስት አውታረ መጠን ስለሚሆን “አይቻልም” ብሎ መከራከሩ ትክክል አይሆንም፡፡

አንድ ሰው እንቅስቃሴ ላይ ሲሆን በአራት አውታረ መጠን ላይ እንዳለ ነው የሚታመነው። ውሻችንን በሰንሰለት አስረን በመንገድ ስንሄድ የሰንሰለቱ እርግብግቢት ወይም መሽከርከር ምን ይመስላል? የውሻው፣ የጌታው የኮቴና የእግር እንቅስቃሴስ? ሁለትና ሦስት አውታረ መጠንን ለማሳየት የውጭ አገር ሰዓሊያን ብዙ ማሳያ አቅርበዋል፡፡ እኔ የማልቀበላቸው አሉ፡፡ ከአገር ውስጥ በደብረብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን፣ በአባ ዘወልደማርያም ማሞ የተሳለውንና ከውጭ አገር ደግሞ የሚካኤል አንጀሎንና የመሳሰሉትን የተለያዩ ማሳያዎች በምስል አስደግፎ በማቅረብ ማብራራቱን የቀጠለው ሰዓሊው፤ “የምናየው ነገር በትልቅና በትንንሽ መስመሮች የተወሰነ ነው፡፡ አንድ ቀለም ቅብ እኛ ማየት በቻልነው መጠን ነው የሚገለፀው፤ በአጉሊ መነጽር ማየትና በነፃ ዓይን ማየት የተለያየ ነው” ብሏል፡፡ አውሮፓውያን ‘ህዳሴያችን’ በሚሉት ዘመን ስዕል የሚገለፀው አንድ ሰው አንድን ነገር በመስኮት እንደሚያይ ተደርጐ ነበር ያለው ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤ በመስኮት ማየቱን ትቶ፣ ከቤት ወጥቶ ማየት አይቻልም ወይ? በሚል ያነሳሁት ጥያቄ በ “ንግስ” ኤግዚቢሽን ያቀረብኳቸውን ስዕሎች ለመስራት አስችሎኛል ብሏል፡፡

ስዕሎቹ በልጅነት ትዝታዎቼ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ የአለቶቹ ትልቅነት በዚያ ዘመን እይታዬ በውስጤ የተቀረፁ ናቸው፡፡ ዛሬ ሄጄ ሳያቸው ያን ያህል አይገዝፉም፡፡ ጥልቀትን ወደ ውስጣችን ለማምጣት፤ ሁሉም ሰው ከፍታ ቦታዎችን መውደዱን፤ የከሰል፣ የችቦ፣ የኤርታሌ…ግለትን ለማሳየት የሳልኳቸው ናቸው፡፡ አለቱን ወይም የምስላቸውን ነገሮች ከፍሬም ውጭ አድርጌ የመጠቀሜ ዋነኛ ምክንያትና መነሻ በጥንታዊ የአገራችን ስዕሎች ያየሁት አሳሳል ነው፡፡ በኤግዚቢሽኑ ካቀረብኳቸው ስዕሎች መካከል “ንግስ” ከሌሎቹ ጋር የሚያያዝ ነገር የለውም። በወጣትነቴ ትልቅ ሥራ እሰራለሁ የሚል ሕልም ስለነበረኝ ያንን ምኞቴን ያሳካሁበት ሥራ ነው፡፡ “ንግስ”ን ለመሳል 3 ዓመታት ጠይቆኛል፡፡ የሰዎቹና የአልባሳቱ ብዛት ብዙ ጊዜ ከወሰዱብኝ ምክንያቶች ዋናው ነው ብሏል፡፡ ሰዓሊ መዝገቡ፤ የውይይት መነሻ ሀሳቡን አቅርቦ ሲያጠቃልል፤ የጥያቄ፣ የሙገሳና የአስተያየት መስጫ ሞቅ ያለ መድረክ ተከፈተ፡፡ ከእነሱም መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት፡- ከጣሊያን ወረራ በኋላ የመጡ ኢትዮጵያዊ ሰዓሊያን ዘመናዊነትን አገራዊ ለማድረግ ሞክረዋል። የኢትዮጵያውያኑን ሥራ ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ሰዓሊያን ሥራዎች ጋር ብናወዳደር ጫና እንዳላረፈባቸው እናስተውላለን፡፡ የመዝገቡ ተሰማ ሥራዎችን ስንመለከት ደግሞ በአገራዊ መሠረት ላይ የመጨረሻውን ማህተም አኑሮልናል፡፡ በ1920ዎቹ የጀመረው ኢትዮጵያኢዝም ከሌሎች ተነጥሎ ወጥቶ በራሱ ማደግ መቀጠሉን የመዝገቡ ሥራዎች ያረጋግጣሉ፡፡ በሰለጠነው ዓለም ከሌሎች ጋር በእኩል ሁኔታ መሰለፍ እንደሚችል አረጋግጧል።

በዲጂታል ካሜራዎች ብቻ ሊቀረፁ የሚችሉ ምስሎችን በስዕል ሸራው ላይ መሳል የቻለው መዝገቡ፤ በ100 ዓመት የሥነ ጥበብ ታሪካችን ውስጥ አዲስ መንገድ ፈጥሯል፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊ ስዕልና አሳሳልን የሚመራው ማነው? የሚለው ጥያቄ የሚያጓጓ ቢሆንም መልሱን ለጊዜ እንተወው፡፡ እንደ መዝገቡ ተሰማ በድንቅ ሥራዎቻችን ምሳሌ መሆን ከቻልንና ለሥነ ጥበብ ጥናት ሰፊ ጊዜ ከሰጠን በመስኩ ፈጣን ዕድገት ይመዘገባል፡፡ በእኛ ሙያ ውስጥ አቅጣጫዎች አሉ ከተባለ አንዱ አቅጣጫ የመዝገቡ ተሰማ ነው፡፡ ግርማ ይፍራሸዋ በፒያና ሙዚቃ፣ መዝገቡ ተሰማ በቀለም ቅብ ሥራዎቻቸው ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝተዋል። በጥረትና ትጋት እዚህ የደረሰ ወጣት ሰዓሊ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ተመኝተን አቅቶናል፡፡ በሌሎች አገራት ሰዓሊያን ማዕረግና ስልጣን አላቸው፡፡ በእኛ አገር ሰዓሊ ከትምህርት ቤት ከተመረቀበት እስከሚሞትበት ዕለት ድረስ ሰዓሊ ተብሎ ነው የሚታወቀው፡፡ አፈወርቅ ተክሌ በአገራቸው መዝኖ የሚያከብራቸው ስላጡ ፈረንሳይ ሄደው ራሳቸውን ስላስተዋወቁ “ሎሬት” ተባሉ፡፡ ትርጉሙ ክብር የሚገባው ማለት ነው፡፡ መዝገቡ ተሰማም ክብር የሚገባው መባል አለበት። ዓይን ያለኝ ይመስለኝ ነበር፡፡

ዓይኔን የከፈተልኝ መዝገቡ ተሰማ ነው፡፡ ክብር መስጠትን በተመለከተ የተሰጠ አስተያየት አለ፡፡ በቀድሞ ዘመን ለኪነ ጥበብ ሰዎች የሚሰጥ ሊቅ፣ ሊቀ ጠበብት፣ ሊቀ ሊቃውንት … የሚባሉ ማዕረጎች ነበሩ፡፡ ያ በጎ ጅምር ስላልቀጠለ ነው አንዱን ባለሙያ ከሌላኛው መለያ ያጣነው፡፡ በስዕሎቻቸው ብዥታን ለማጥፋት ብዙ የለፉ ሰዓሊያን አሉ፡፡ በብዥታ ውስጥ መንፈሳዊ ርዕሰ ጉዳዮችን ልታያቸው ያልሞከርከው ለምንድነው? ስዕሎቹ እንደማይሸጡ ገልፀሀል፡፡ ዕጣ ፈንታቸው ምንድነው የሚሆነው? ለአገር ውስጥ ከሆነ ስዕሎችህን በቅናሽ እንደምትሸጥ አውቃለሁ፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲገዛህ ብታደርግ … አገራቸውን በለምለምነቷ፣ በሰቆቃዋ … የሚገልጿት አሉ፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን ላቀረብካቸው ሥራዎች መነሻህ ምንድነው? ድንጋይና አለቶቹ የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማሳየት ይሆን? እንስሳቱን በቋጥኝና በድንጋያማ ቦታዎች ያኖርካቸው ምን ልትነግረን ፈልገህ ነው? ስዕሎችህ ላይ የበዛ ፀጥታ መስፈኑ ይታያል፡፡ ሰዎችም፣ እንስሳት ላይም ፀጥታ ጎልቷል፡፡

ሌላው ቢቀር በ“ንግስ” ስዕል ላይ አንዲት ሕፃን ስታጨበጭብ ከምትታየው በስተቀር ፀጥ ያለና ያልተለመደ የሚመስል ሥነ ስርዓት ነው። ምክንያትህ ምንድነው? ለመዝገቡ ከቀረቡት ጥያቄዎች ለአንድ ሁለቱ እኔ ምላሽ አለኝ፡፡ ሰዓሊው ሀሳቡን በሸራዎቹ ላይ ዘርግፏል፡፡ በስዕሎቹ ላይ የሚታየው ሰላምና ፀጥታ በመዝገቡ ውስጥ ያለውን እርጋታ አመልካች ነው። ታሪካችን በጦርነት የተሞላ ቢሆንም ለመዝገቡ ሰላምና ፀጥታው በዝቶ ታይቶታል፡፡ እነዚህን መሰል ጥያቄዎች አስተያየትና ሙገሳዎች ከቀረቡ በኋላ ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ የማጠቃለያ ሀሳቡን አቅርቧል፡፡ የዓለማችን ብዙ ሰዓሊዎች ማዕረግ የላቸውም ያለው መዝገቡ፤ ባለ ማዕረግ ባለመሆኔ ችግር የለውም ብሏል። ከመንፈሳዊ ጉዳይ ጋር ለተነሳው ጥያቄም በሁለቱም አቅጣጫ ድብቅ አለሞች እንዳሉ፤ የሰው ልጅ የማየትና የመረዳት አቅሙም ውስን መሆኑን ገልጿል፡፡ ተፈጥሯችን ከሰጠን በላይና በታች አናይም፤ ጆሯችን ከሚችለው በላይ ሙዚቃ አናዳምጥም። የእይታ አቅማችንን ለማጉላት ሳይንቲፊክ ማይክሮስኮፕ እንደምንጠቀመው ሁሉ አንዳንድ ሰዓሊያንም ሥራዎቻቸውን በአብስትራክት የሚያወሳስቡት ስሜትና ሀሳባቸው ለመግለጽ ከመጨነቅና ከመጓጓት ነው፡፡

የስዕሎቹ የነገ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን እኔም አላውቅም፡፡ የሚያግዘኝ ካገኘሁ በተለያዩ ቦታዎች ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት ለሕዝብ ባሳይ ደስ ይለኛል። እያንዳንዱ ስዕል የራሱ የሆነ ዕድል አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ “ሰቆቃውን ዘመን እኔም አልፌበታለሁ። ሁላችንም በዕድሜ ዘመናችን በተለየ የምናስታውሰው ወርቃማ ጊዜ አለን፡፡ የእኔ ወርቃማ ዘመን እስከ 16 ዓመቴ በትውልድ ቀየዬ የቆየሁባቸው ጊዜያት ነበሩ። በኋላ በግልም፣ በጋራም፣ በቤተሰብ ደረጃም … ብዙ ችግር አሳልፌያለሁ፡፡ ካሳለፍኩት ችግር ይበልጥ የወርቃማ ዘመን ትዝታዎቼ በስዕል ሥራዎቼ ላይ ጎልተው ወጥተዋል፡፡ ከመናገር ይልቅ ዝምታ የተሻለ ዋጋ የሚኖረው ጊዜ አለ፡፡ በ “ንግስ” ስዕል ላይም ፀጥታ ሰፍኖ የሚታየው ያችን የፀጥታ ቅጽበት ጠብቄ ስለሳልኩት ነው፤” በማለት የማጠቃለያ ሃሳቡን ቋጭቷል፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 07 December 2013 12:53

ሽፋኑ የጋረደው መጽሀፍ

ድሮ ድሮ ክረምት በመጣ የምልበት ምክንያት ከትምህርት ቤት መዘጋት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን እረፍት በመናፈቅ ነበር፡፡ አሁን አሁን ክረምቱን ከምናፍቅባቸው ምክንያቶች አንዱ ከመፃህፍት ህትመት ጋር የተያያዘ እየሆነ መጥቷል። አመቱን አድፍጠው የቆዩ መጻህፍት በክረምት ብቅ ማለታቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ ከእረፍት ቀናት በአንደኛው የክረምት ሲሳይ ከሆኑ መፃህፍት አንደኛው በእጄ ከገባ ቆየ፡፡ የመፃህፍት አዟሪው ደንበኛዬ “ቀሽት የሆነ ስለቺክ የሚተርክ መጽሀፍ” ብሎ አቀበለኝ፡፡ ያቀበለኝ መጽሀፍ ርዕስ እንግዳ አልሆነብኝም፡፡ በሽፋኑ ዙሪያ በማህበራዊ ድረ ገፆች (ፌስቡክ) ላይ የሞቀ ክርክር አድርገናል፡፡ አንድ ወዳጄ በፌስቡክ ገፁ ላይ ሽፋኑን ለቆት ስለነበር፣

በዚሁ መነሾ ከጓደኞቻችን ጋር ስንነጋገር ቆይተናል፡፡ (በነገራችን ላይ በፌስ ቡክ መፃህፍትን ማስተዋወቅ እጅጉን ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ፌስ ቡክን ለቁም ነገር ማዋል ይኼ ነው!) … በመጽሀፍ ሽፋን ላይ የሴትን ልጅ ዳሌ አጉልቶ በማሳየት፣ ከጭን ጋር በተያያዘ በተሰጠው የመጽሀፉ ርዕስ … ዙሪያ ኩነና የበዛበት ውይይት አደረግን፤ እውነት ለመናገር ከኮናኞቹ መካከል ዋነኛው እኔ ነበርኩ፡፡ … እና ከመፅሀፍ ሻጩ ደንበኛዬ የተቀበልኩትን መፅሀፍ እንደቀልድ ገለጥ አድርጌ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ … ማቆም አቃተኝ!!! “ውሸትን ፍለጋ …” የሚለው መፅሀፉ መግቢያ ላይ የተሰደረው አጭር ትርክት በግርምት አንገቴን እንድወዘውዝ አደረገኝ፡፡ እንዲህ በመሰለ የሚገርም የታሪክ አውዶች ለተከበበ መጽሀፍ የተመረጠለት የሽፋን ምስልና የመጽሀፉ ርዕሰ ጭምር ተገቢ ናቸውን? ብዬ እንድጠይቅ ሆንኩኝ፡፡

“የመጀመሪያው ጫማ…” የሚለው የመጽሀፉ ሁለተኛ አጭር ትርክት ስለ መጽሀፉ ሚዛን ደፊነት እንዳረጋግጥ አደረገኝ። ይኼ ሁሉ ሲሆን መፅሀፉን ከመጽሀፍ አዟሪ ወንድሜ አልገዛሁትም ነበር፤ ታሪኮቹ አጫጭርና በአንድ ትንፋሽ የሚጨረሱ አይነት ስለሆኑ እሱም አልተከፋብኝም፡፡ የማታ ማታ መጽሀፉን ገዝቼ በቅርብ ባገኘሁት የአንድ ካፌ ወንበር ላይ አረፍ ብዬ ማንበቤን ቀጠልኩ፡፡ “ኩመላና ሊቀመንበር መንግስቱ” የሚለውን ትርክት ሳነብ ውስጤ በጥያቄ ጠነከረ፡፡ ትርክቱ ከጨርቆስ የካቲካላ መንደር ተነስቶ፣ በፕሬዚዳንት መንግስቱ ቤት በኩል አድርጎ … የህይወትን ነፀብራቅ የሚያሳይ ግሩም ስራ ነው፡፡ ህይወትን ከጭቃ አቡኪነት አንፃር የሚመረምረው ይኼው ትርክት፤ አንድ ጭቃ አቡኪ በራሱ ዓለም ውስጥ እየኖረ የሚያጋጥመውን የኑሮ ሁነት የሚያስቃኝ ነው። ስንት ሰዎች አሉ በራሳቸው ህይወት ዛቢያ ላይ የሚሽከረከሩ? ስንት ሰዎች አሉ የህይወት ግባቸው የተሰጣቸውን ህይወት መኖር ብቻ የሆነ … እያልኩ በሀሳብ እንድማስን ያደረገኝ ሥራ ነበር፡፡ ከዚሁ በተፃራሪው በህይወት ያሉ ሰዎችን (ሊቀመንበር መንግስቱንም ሆነ ባለቤታቸው ወ/ሮ ውባንቺ ቢሻውን) መጽሀፉ ውስጥ ማካተቱ ተገቢ መስሎ አልታየኝም፡፡ የኔ ነገር … ስለመጽሀፉም ሆነ ስለ ደራሲው ሳልናገር ዘልዬ ስለ ይዘቱ ማውራት ጀመርኩ አይደል? የመፅሀፉ ርዕሰ “በአራጣ የተያዘ ጭን” ይሰኛል፡፡ ደራሲው ደግሞ ዮፍታሔ ካሣ፡፡ በሊትማን ጀኔራል ትሬዲንግ አማካኝነት የሚከፋፈል መጽሀፍ ሲሆን፤ 234 ገፆች አሉት። እንደምታዩት የመፅሀፉ ሽፋን ላይ ሞንዳላ ሴት ትታያለች፡፡ ከመጽሀፉ ርዕስ ጋር የሽፋን ፎቶውን ስታስተያዩ የሚመጣባችሁ ምስል “ሮማንቲክ” እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡

የተለመደ የገበያ ጫጫታ ለመፍጠር እንደሚሞክሩ መጽሀፍት አድርጋችሁ ብትወስዱትም “ለምን?” የሚል አይኖርም፡፡ ምክንያቱም በዚህ መልኩ የቀረቡ መጻህፍትን ተሻምተን ገዝተን ቆሽታችንን ያሳረርንበት ጊዜ በዛ ያለ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ይህን የመሰለ የፅሁፍ በረከት በሽፋኑ “ቀሽምነት” ሳይነበብ ቢያልፍ ኪሳራው የጥበብ ጭምር ነው፡፡ መፅሀፉን በአንድ ትንፋሽ “ጭልጥ” ካደረግሁት በኋላ ጠቃሚ ሀሳብ ለምን አላነሳም በሚል ስሌት ይኼንን ጽሁፍ ወደ ማዘጋጀቱ ገባሁ፡፡ “በአራጣ የተያዘ ጭን” 19 ትረካዎችን ይዟል፡፡ ዳጎስ ያለው “ስድስት ኪሎ ካምፓስ” የሚለውና መቼቱን በስድስት ኪሎ ካምፓስ ያደረገው ትረካ ነው፡፡ ትረካው ከተለመደው የዩኒቨርስቲ ህይወት አፃፃፍ በተለየ መልኩ፤ የዩኒቨርስቲ ህይወት ከከባቢው ማህበራዊ ህይወት ጋር ያለውን መስተጋብር ለማነፃፀር ሞክሯል፡፡ ሙከራው ግን ብዙም የተሳካ አይመስልም፡፡ የዚህን ትርክት መሰረታዊ ጭብጥ ለማግኘት ብባዝንም ይህ ነው የሚባል ጭብጥ ለማግኘት አልታደልኩም፡፡

ይልቁንም በዘፈቀደ የተፈጠሩ በሚመስሉ ገፀ-ባህሪያት ፈገግ የሚያሰኙ እና ዘና የሚያደርጉ የዕለት ገጠመኞች ፈታ ብያለሁ። እንደኔ እንደኔ የመጽሀፉ ደራሲ የ6 ኪሎ ካምፓስ የሚለውን ትረካ ሲጽፍ ስሜቱን ከመከተል ውጪ እኛን አንባቢዎቹን ያሰበን አይመስለኝም። አንባቢው ይኼንን ጽሁፍ ሲያነብ ከመዝናናት ውጪ ምን ጭብጥ ያገኝበታል የሚለው ብዙም አላስጨነቀውም፡፡ ይህ ሁኔታ ምናልባት የዘመናዊ ልቦለድ አፃፃፍ መሰረታዊ መርህ እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ ዊልያም ብሩስለን የተባሉት እንግሊዛዊ ሀያሲ፤ ይኼንኑ የሚያጠናክር ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ እንዲህ ይላሉ … The authors of the modern short story “no longer attempt to make daily life more entertaining by inventing exotic plots. Instead, modern short story writers have tended to base their narratives on their own experience; here the focus is much more on the less spectacular aspects of life, on the significance underlying what is apparently trivial. The result of such perceptive writing is perfection of form, harmony of theme and structure, and precision of style to reveal the subtleties of the human mind and of human behaviour. (የዘመናዊ አጭር ትረካ ፀሀፊዎች አዳዲስ የህይወት ዘይቤዎችን እና መሳጭ የሆኑ የታሪክ መዋቅሮችን ለመፍጠር ላይ ታች የሚሉበት ጊዜ አብቅቷል፡፡ ይልቁንም ዘመናዊ ጸሀፍቱ በራሳቸው የህይወት ልምምድ ላይ ይመሰረታሉ፤ ይህ ልምምድ በህይወት ያልታዩ ገፆች ላይ ያተኮረና ተራ ተርታ የሚባል ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ አፃፃፍ ይትብሀል ውጤት ደግሞ የቅርፅ ፍፁምነትን፣ የጭብጥ አለመዛነፍን እንዲሁም የሰውን የህይወት እና የህሊና ስርቻ እንዲሁም የባህሪ ውስጠት የሚገልፅ ይሆናል።) መጽሀፉ ላይ ያገኘሁት ትልቁ ነገር ግጥም መሰል የአጭር ልቦለድ አፃፃፍ ይትብሀልን ነው። በመጽሀፉ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ትረካዎች እንደ ግጥም በአንድ ቁጭታ የሚያልቁ፣ እንደ ግጥም ምጥንነት የሚታይባቸው፣ እንደ ግጥም የማይሰለቹ ናቸው። There is a close connection between the short story and the poem as there is both a unique union of idea and structure. የሚለውን የአንዳንድ ምሁራን አተያይ ያረጋገጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለነገሩ በመጽሀፉም ውስጥ ግጥምን ከአጭር ትረካ ጋር አሰናስሎ የማቅረብ ቅርጽ አስተውያለሁ፡፡

“የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ ተስፋዬ ገብረአብ እንደተጠቀመበት ያለ ማለት ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ይህ አይነቱ የአፃፃፍ ቅርፅ ከሁለቱም የአፃፃፍ ዘውጎች የሚገኘውን ኪነታዊ እርካታ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ልክ ሙዚቃዊ ድራማ በነጠላው ከሚቀርብ ድራማ በበለጠ የመግለጽ እና ኪነታዊ ለዛው ከፍ እንደሚል ሁሉ፡፡ ለዚህ አባባል ዋቢ ካስፈለገ በመጽሀፉ ውስጥ “ሴትን ተከትዬ…” የሚለው ትርክት ማሳያ ይሆናል፡፡ “ሴትን ተከትዬ …” የሁላችንንም የልጅነት ህይወት የሚተርክ፣ አንድ ወጣት በሴት ልጅ ፍቅር ልቡ በተሞላበት ወቅት ሊደርስ የሚችልበትን ከፍ ያለ ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዛ ሁሉ በላይ ፀሀፊው የተከተለው የአፃፃፍ መንገድ፣ የአገላለጽ ውበት፣ የአቀራረብ ቅርፅ … ለኔ የተለየ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በአማርኛ የአጫጭር ትረካዎች ውስጥ ብርቅ የሆነብን የታሪክ ድርቀት፣ የቋንቋ ስብራት … “በአራጣ የተያዘ ጭን” ውስጥ ታክሞ እናገኘዋለን። አንድ ወጣት ጸሀፊ “የአማርኛ ትረካዎቻችን በጣም ስለሚጎተቱ ታሪካቸው እንዲፈጥንልኝ እያነበብኩ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ እገባለሁ፤ ፍጥነት ባገኝ ብዬ” ብሎ ነበር፡፡ በዚህ መጽሀፍ ውስጥ የትረካው ፍጥነት እጅግ ከመሰጡኝ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው። ፍጥነቱ ግን የመዋከብ ሳይሆን የመዝናናት ስሜት ይፈጥራል፡፡ እንደ ድክመት የማነሳው ከመግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት የመጽሀፉ ሽፋን እጅግ አወዛጋቢ ሆኖብኛል፡፡ ለምን ዓላማ እንደዚያ ማድረግ እንዳስፈለገ እራሱ አልገባኝም፡፡

የአንድ ሴትን ገላ በማየቱ ብቻ መጽሐፉን የሚገዛ “ጅል” አንባቢስ ይኖር ይሆን? እንጃ ለኔ ግን አይመስለኝም! ከዛ ውጪ በመጽሀፉ ውስጥ የሚታየው የፊደላት ግድፈት የአርትዖት ሥራውን የይድረስ ይድረስ ያስመስለዋል። ቀጣይ ህትመቶች ላይ እነዚህ ነገሮች ቢታዩ፡፡ በማጠቃለያነት፡- A short is a piece of prose fiction which can be read at a single sitting. ታዋቂው አሜሪካዊ ደራሲ ኤድጋር አላን ፖ የተናገረው ነው፡፡ ለኔ ግጥም እና አጭር ልቦለድን ማጣጣም ከሌሎች የስነፅሁፍ ቅርፆች ይበልጡብኛል። በአንድ ቁጭታ የምጨርሰው ነገር ስለምፈልግ ይሆናል። እንጃ ብቻ … በአሁኑ ጊዜ እንደአሸን የፈሉ በሚያስብል ደረጃ የግጥም መፃህፍት በቀናት ልዩነት በሚወጡበት ከተማችን፤ የግጥምን ያህል ባይሆንም የተሻለ የረጅም ልብወለድ ስራ እየተበረከተ ባለበት ወቅት፤ የአጫጭር ልቦለድ እና ትረካዎች መጽሀፍት ከገበያ መውጣት የሚያነጋግር ነው፡፡ ሀሳብ ያለው አንድ ሁለት ቢል ጥሩ ነው፡፡ … በተረፈ የጀመሩትን ስናበረታታ የሚሞክሩት ይጀምራሉና ነውና ዮፍታሔ ካሳ ባለህበት በርታልን!!! በአንድ መጽሀፍ ብዕርህን አስትቀል (ከመፅሀፉ ባገኘሁት አባባል) እሰናበታለሁ!

Published in ጥበብ

በወርሃ ታህሣሥ፣ 2001 ዓ.ም ነው … አንዲት ቀይ የቤት መኪና፣ ስድስት ኪሎ ከሚገኘው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ፣ በአንደኛ በር በኩል ወጥታ ቁልቁል ወደ አራት ኪሎ አቅጣጫ ከነፈች፡፡ የጣሊያኖችን የግፍ ጭፍጨፋ ከሚዘክረው ሀውልት ጋ ሥትደርስ፣ ወደ ማርቆሥ ቤተክርሥቲያን ታጠፈችና አሁንም ቁልቁል ወደ አፍንጮ በር ተተኮሰች፡፡ ሰዓቱ፣ 11፡45 አካባቢ እንደነበረ አሥታውሣለሁ፡፡ ቀዩዋ መኪና፣ የዩኒቨርሲቲው አንድ አንጋፋ መምህር እያሽከረከሯት ወደ ፒያሳ አመራች፤ የመምህሩን አምስት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ብትጭንም፣ ከ12፡30 በፊት፣ አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴዝ ግቢ የማድረስ ሀላፊነት ተጥሎባታል፡፡ ቀይዋ መኪና ከተቆረጠው ሰዓት በፊት ጥቂት ደቂቃዎችን ቀድማ ከተባለው ቦታ አደረሠችን፡፡ የአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴዝ ግቢ፣ ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በወጡ ሙዚቀኞች እንደተቋቋመ በተነገረለት “ሃራ ሳውንድ ባንድ” አማካኝነት፣ ሞቅ ደመቅ ብሎ ይታያል፡፡ በመሣሪያዎች ብቻ የተቀናበሩ ጣዕመ ዜማዎች ይንቆረቆራሉ፡፡

ውጭ ላይ የተሠናዳው መድረክ፣ በህዝበ አዳም ተሞሽሯል፡፡ አሁን ጨለማው ዐይን ያዝ ከማድረግ አልፏል፤ ትላልቅ ፓውዛ መብራቶች መድረኩን በብርሃን አድምቀውታል፡፡ የሙዚቃ ቅንብሩ በስፋት መደመጥ ያዘ፡፡ አንድ ገጣሚ መድረኩ ላይ ወጥቶ በመሣሪያ ቅንብር ከሚወጣው ጣዕመ ዜማ ጋር በወጉ ተለክቶ የተሠፋ የሚመሥል የሰውነት እንቅስቃሴ ማሣየት ጀመረ፡፡ የውዝዋዜው ሥልት፣ ከሙዚቃው ምት ጋር በእርጋታ እየተዋሀደ ከለብታ ወደ ሞቅታ ሲዛወር፣ የገጣሚው አንደበት ተከፈተ፡፡ ከዚያ ሥልጡን አንደበት ውስጥ የሚወጡ የተመጠኑ የስንኝ ቋጠሮዎች፣ በተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ምጣኔ ዜማ ታጅበው ሲለቀቁ፣ በታላቅ ኪናዊ የመንፈስ ከፍታ ወደ ሰማየ ሰማያት የሚያርጉ ይመስሉ ነበረ፡፡

እኔ በበኩሌ ግጥም፣ ከዋሽንት ባለፈ በተለያዩ ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ቅንብር ታጅቦ ሲቀርብ ሣይ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ በመድረኩ ላይ የተለያዩ ወጣት ገጣሚያን፣ ከሙዚቃው ምት ጋር የስንኞቻቸውን ምት እያዋደዱ በውዝዋዜ ሞሽረው ታዳሚውን ማስኮምኮም ቀጥለዋል፡፡ መሀከል ላይ ይመስለኛል፣ የቀዩዋ መኪና አሽከርካሪ፣ አንጋፋው የዩኒቨርሲቲ መምህርም መድረኩን ተቆጣጠሩት፤ ገጣሚው ፕሮፌሰር፣ ከወጣቶቹ ባልተናነሰ፣ እንደውም ካንዳንዶቹ በተሻለ ቆሞ ሲያሥተምር የዋለ ወገባቸውን ከሙዚቃው ሥልት ጋር አዋደው ማወዛወዝ ጀመሩ፡፡ ግጥማቸውንም ከሙዚቃው ሥልት ጋር እያዋሀዱ አቀነቀኑት፡፡ ይህ ቀን፣ በኢትዮጵያ የሥነ ጽሁፍ ታሪክ፣ ሥርዓት ባለው መልኩ ግጥም በጃዝ የቀረበበት ዕለት ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እንደማስታውሰው ከሆነ፣ በዕለቱ ግጥሙን በመሣሪያዎቹ ቅንብር ጣዕመ ዜማና በራሡ ሥልታዊ ውዝዋዜ አጅቦ በማቅረብ መድረኩን የሟሸው ገጣሚ አበባው መላኩ ይመስለኛል፡፡

“ይመስለኛል”ን ያመጣሁት፣ የመጀመሪያው የመድረክ አሟሺ አበባው ነው ወይስ ደምሰው መርሻ? ባለ “አሻራ”ዋ ምሥራቅ ተረፈ ናት ወይስ ሰዓሊዋ ምህረት ከበደ? ወይስ ደግሞ “ለግጥም ጥም ጠብታ” የበቃው ፍሬዘር አድማሱ? የሚለውን ቀዳሚ ሰው በውል ማስታወስ ባለመቻሌ ነው፡፡ “እየሄድኩ አልሄድኩም” የሚሉት የቀዩዋ መኪና አሽከርካሪ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ግን መሀከል ላይ ማቅረባቸው፣ ብዙ ጥርጣሬ አልፈጠረብኝም። ለማንኛውም ግን፣ ስድስቱ ገጣምያን የዕለቱ ባለ ታሪኮች እንደነበሩ ለመጠቆም መፈለጌን ብታውቁልኝ አልጠላም፡፡ በርግጥ፣ ግጥም በጃዝ ሥርዓት ባለው ቡድናዊ አደረጃጀት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው በ2001 ዓ.ም ነው ቢባልም፣ ለዚህ የቡድን ዝግጅት ከመብቃቱ በፊት ሌሎች ሙከራዎች እንደነበሩ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እስከ አሁን በተገኙ ማስረጃዎች መሰረት፣ በ2000 ዓ.ም በብሔራዊ ትያትር አበባው መላኩ “ቅናት” የተሠኘ ግጥሙን በሲዲ በቀረበ የሙዚቃ ቅንብር አጃቢነት ለተመልካች ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዕለት ከታዳሚው ከፍተኛ አድናቆት እንደተቸረው ተነግሯል፡፡ አበባው፣ በብሔራዊ ትያትር መድረክ ግጥሙን ከተቀናበረ ሙዚቃ ጋር ያቀርብ ዘንድ ንቃትና ብርታት የሆነው “ደግ አይበረክትም” የተሠኘው የግጥም ሲዲው ዝግጅት ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡

እንግዲህ፣ ግጥምን በጃዝ መድረክ የሚያቀርበው የቡድን አባላት በአሊያንሥ ኢትዮ-ፍራንሴዝ ዝግጅትና በኋላም በተለያዩ መድረኮች ግጥም በጃዝ ማቅረቡን እየሠለጠነበት መጣ፡፡ ቡድኑ፣ ከታዋቂው የፒያኖ ተጫዋች ግርማ ይፍራሸዋ ጋር በጣሊያን የባህል ማዕከል ያቀረበው ዝግጅት፣ የወደፊቱን የከፍታ ዘመን አመላካች ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ በቦሌ ሮክና በሸራተን አዲስ መድረኮች ላይም ኢትዮጵያዊ ግጥም በጃዝ ተሞሽሮ ይቀርብ ዘንድ የቡድኑ የላቀ ትጋትና ጥረት ቀጠለ፡፡ በ2003 ዓ.ም፣ ወር በገባ የመጀመሪያው እሮብ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል መድረክ ላይ ከመለከት ባንድ ጋር በኋላም ከአቢሲኒያ ባንድ ጋር በመተባበር ግጥም በጃዝ እየሸመኑ ማቅረብ ተወዳጅ ኪነት እየሆነ መጣ። የዋቢ ሸበሌው የአንድ ዓመት የግጥም በጃዝ ጉዞ ሲስተናበር የነበረው በቸርነት ወልደ ገብርኤል፣ በደምሰው መርሻና በአበባው መላኩ እንደነበረ ያሠባሠብኳቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚሁ ዓመት ወደ ኋላ ላይ ግሩም ዘነበና ሜሮን ጌትነት የቡድን አባላቱን እንደተቀላቀሉ ሰምቻለሁ፡፡ አሁንም የግጥም በጃዝ መድረኮች፤ የታዳሚን ቀልብ እየገዙ፣ የኪነት ልክፍት ያለበትን እያፈዘዙ፣ የገነገኑ ሀገራዊ ሰንከፎችን እየመዘዙ የስኬት ጉዟቸውን ተያያዙት፡፡ በ2004 ዓ.ም፣ ግጥም በጃዝ በራስ ሆቴል መድረኮች ላይ አብቦ ይፈካ ዘንድ ጊዜው ፈቀደ፡፡

ወር በገባ የመጀመሪያው እሮብ የራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ፣ በታዳሚዎች መጣበብ ጀመረ። የሆቴሉ ሰፊ ግቢ ሊሸከመውና ሊያስተናግደው ከሚችለው በላይ በሆኑ ረዣዥም ሰልፎች ይፈተን ዘንድ ግድ አለው፡፡ አዳራሹ፣ ከ800 በላይ የሚሆኑ ታዳሚዎች ጢም ብለው ሞልተው ይፈሡበታል፡፡ የሚገርመው ግን ይህ ሁሉ ታዳሚ የሚርመሰመሰው ዝግጅቱ የሚቀርበው በነፃ ሥለሆነ እንዳይመሥልዎ! 50 ብር የመግቢያ ዋጋ ለመክፈል የተሠለፉ የግጥም በጃዝ እድምተኞች፣ አዳራሹ እየሞላባቸው ሲመለሱ ማየት የየዕለቱ ክሥተት ሆኗል፡፡ የራስ ሆቴሉ ግጥምን በጃዝ መድረክ አሠናጂ የቡድን አባላት፣ ለግዜው “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” በሚል ሥያሜ፣ ድርጅት ከፍቶ የኢትዮጵያን ግጥም በጃዝ አፍክቶ ማቅረቡን ተያይዞታል፡፡ በራስ ሆቴል መድረክ ወር በገባ በመጀመሪያው ዕለተ እሮብ፣ ለጥበብ ሱሰኞች ምሣቸውን እያደረሠ ይገኛል። የቡድኑ የጥበብ ጉዞ ሥርዓት ባለው መንገድ እየተጓዘ፣ ለተከታታይ 28 ወሮች በመድረክ ላይ ነግሷል፡፡

ቡድኑ፣ ዝግጅቱን በተከታታይ ማቅረብ የጀመረበትን ሁለተኛ ዓመትም ለማክበር በቅቷል፤ በዚሁ በዓል ላይ፣ የተመረጡ ዝግጅቶች፣ “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” (ቅጽ አንድ) በሚል ስያሜ በዲቪዲ አሣትሞ በ50 ብር ዋጋ ለጥበብ ወዳጆች ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ በነገራችን ላይ በራስ ሆቴል መድረክ በጃዝ የሙዚቃ ቅንብር ተከሽነው የሚቀርቡት ግጥሞች ብቻ አይደሉም፤ ስሜት ኮርኳሪ፣ መሣጭና እውቀት አጋሪ የሆኑ ወጐችና ዲስኩሮችም ሢቀርቡ አይቻለሁ፡፡ እንደውም፣ በጦቢያ ግጥምን በጃዝ ቢሮ ውስጥ በተገኘ መርሐ ግብር መሠረት፣ በየዕለት መድረኩ 5 ገጣምያን፣ 1 ወግ ተራኪ እና1 ዲስኩር አቅራቢ የኪነት ቤተኞች ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ይታወቃል፡፡ የዛሬ የጦቢያ ግጥም በጃዝ ቡድን ተጠሪዎች፤ አበባው መላኩ፣ ምሥራቅ ተፈራ፣ ደምሰው መርሻ፣ ምህረት ከበደ፣ ግሩም ዘነበና ሜሮን ጌትነት ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ፣ በዘመነኛ ትንታግ ገጣሚነታቸው ይታወቃሉ፤ በመካከላቸው በትወናም የተጨበጨበላቸው ይገኛሉ፡፡ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ አብዛኞቹ የቡድን አባላት በተለያዩ መድረኮች በግጥም ተናግረዋል፤ ለግጥም ተዋድቀዋል፤ ስለ ግጥም አንብተዋል፤ ስለ ግጥም ቆመዋል፤ ለግጥም ጦም አድረዋል፡፡ ዛሬ ግን በግጥም እያሠቡ፣ በግጥም ትውልድ ይሞግታሉ፤ በግጥም ተከብረው፣ በግጥም በልተው አድረዋል፡፡ ዛሬ ይህ ቡድን፣ ከተለያዩ ኤምባሲዎችና ከተለያዩ ድርጅቶች የአብረን እንስራ ጥሪ ይቀርብለታል። በታወቁ ተቋማት ስፖንሰርነት፣ የተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮችን ይወጣ ይዟል፡፡ ለምሣሌ በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም፣ ከያኒው ሰርክ የሚጠበብበት ተፈጥሮ፣ ህልውናዋ አደጋ ላይ መውደቁን ለማጠየቅ፣ በብሔራዊ ትያትር መድረክ “ጥበብ ለተፈጥሮ” በሚል ርዕስ የተደነቀ ዝግጅት አቅርቧል፤ በዕለቱ የቀረቡት ግጥሞች በ80 የፖሊስ የማርሽ ባንድ አባላት ታጅበው እንደነበረ ይታወሣል፡፡ ዛሬ፣ “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” የቡድን አባላት፣ የራስ ሆቴልን መድረክ በጥበብ አድምቀው የሚሞሸሩት፣ በራሣቸው “የመንፈስ ከፍታ” ያህል ብቻ በመንጠቅ አይደለም፤ የተለያዩ ገጣሚዎችን፣ ወግ አራቂዎችን፣ ዲስኩር አቅራቢዎችን ወዘተ በመጋበዝ አዳዲስ ጥበበ ቃላት እንዲከሸኑ ሥርዓት ዘርግተዋል እንጂ፡፡ ለዚህ ነው፣ ከእግረ ተከል የኪነት ባለሟሎች እስከ ጉምቱ የጥበብ አያቶች ድረስ በመድረክ ላይ ሢዘምኑ የሚታየው፤ በእውነትና በእውቀት እየተመሙ፣ ኪናዊ ውበት ሲያፈልቁ የሚገኘው፡፡ ዛሬ ግጥም በጃዝ መድረክ የሚደነቅና የሚወደድ ውበት ብቻ ሣይሆን የሚናፈቅ ሕይወትም እየሆነ ያለ ይመሥላል፡፡

ዛሬ፣ 50 ብር ከፍለው የሚታደሙ አድናቂዎች ብቻ አይደለም የሞሉት፤ የዓመታት ወጪ ሸፍነው የቡድኑ አባል ለመሆኑ የሚታትሩ ጭምር ተመዝግበዋል እንጂ፡፡ ዛሬ ቡድኑ፣ ጥበብን የሚያቀርብበት የነፃ አዳራሽ መንግሥት ይፍቀድልኝ አይልም፤ እንደውም በየወሩ ለመንግሥት በሺዎች የሚቆጠር ብር ይገብራል እንጂ፤ “ግብር አይደለም ዕዳ” እንዲል የገቢዎች ሚኒስቴር፡፡ ምን አለፋዎት … ግጥም በጃዝ መድረክ ላይ በሃበሻ ግጥም፣ የሀበሻ እውነትና እውቀት በጥበባዊ ሥልት ተፈታትቶ በምርጥ የቃላት ጡብ፣ ሢገጣጠም ያያሉ (እመኑኝ እያጋነንኩ አይደለም-በፍፁም)፡፡ ከሃበሻ የኑሮ ልማድ ውስጥ እውነቱና እውቀቱ በብልሃት ይተነተናሉ-በግጥም፡፡ ከእውነቱና ከእውቀቱ የተጠነፈፈው ማንነቱ በቃላት ምታት መድረክ ላይ ሢሠጣ፣ ታዳሚው እየሣቀ ይተክዛል፤ እያጨበጨበ ይቆዝማል፡፡ ግጥሞቹ፣ ወጉና ዲስኩሩ በሀበሻ የመንፈስ ክር የተሣሠሩ ሽንፈቶቹን፣ ቁጭቶቹን፣ ህልሞቹን ይናገራሉ፤ ከሀገር እውቀቶቹና እውነቶቹ ጋር እየተጣቀሡም፣ የዘመን መንፈስን እያሥጠቀሡ፣ ገዝፈውና በዝተው ይቀነቀናሉ፡፡ የአዳሚም የታዳሚም መንፈስ ከፍ ብሎ ይንሣፈፋል፤ ዝቅ ብሎም ይነፍሣል … እኔ በበኩሌ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነትም በተማሪነትም ያጣሁትን የመንፈሥ ልዕልና በዚያ አዳራሽ ውስጥ የተጐናፀፍኩ አይነት ነው የሚሠማኝ፡፡ የሀበሻ ግጥም፣ ወግና ዲስኩር በተቀናበረ ሙዚቃ ታጅበው እውነት፣ እውቀትና ውበት በሚያፈልቁበት በዚህ አዳራሽ፣ የሰዓታት ሰላም ያገኘሁ ይመሥለኛል፡፡ እስኪ በራሥ ሆቴል አዳራሸ ከሚቀርቡ ዝግጅቶች መካከል የቅርቡን (ህዳር 4 ቀን 2006 ዓ.ም) የጥበብ ድግሥ በጨረፍታ ልጠቁማችሁ። እንደተለመደው ትልቁ አዳራሽ ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሏል፡፡ የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙኃን ባልደረቦች ትላልቅ መቅረፀ ምሥል ካሜራዎችን ተሸክመው ዝግጅቱን ለመቅረጽ ከወዲያ ወዲህ ሽር ጉድ ይላሉ፡፡ “ነፃ አውጪ ባንድ” በመሣሪያ የተቀነባበሩ ጣዕመ ዜማዎችን ያሠማሉ፡፡

የመድረክ አጋፋሪው፣ ዝነኛው ተዋናይ ግሩም ዘነበ ወደ መድረኩ ጐራ እያለ በአስገምጋሚ ድምፁ መርሐግብሩን ያሥተዋውቃል፡፡ በዚህ ዕለት፣ የሸገር ሬዲዮ ባልደረባው ስመ ጥሩ የመድረክ ሰው ተፈሪ ዓለሙ፣ የሁለት ትውልዶችን ብጭቅጫቂ ኑሮ በ “ስውር-ስፌት” እየጠቀመ ያለው (“ጠ” ጠብቃ ትነበብ) የአዲስ አድማሱ ዋና አዘጋጅ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ ሢያሻው በግጥም መናገር የሚችለው ታዋቂው ሰዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን፣ የዕለቱን መድረክ “የመንፈስ ከፍታ” አግዝፎ የናኘው ገጣሚ በረከት በላይነህ፣ ለግጥም ወይም ስለ ግጥም ሕይወተን እየከፈለ ያለ የሚመሥለኝ ገጣሚ ደምሰው መርሻ፣ መሪር ሰዋዊ ግዙፍ ጥያቄዎች በተራኪ ግጥም እንዴት በብልሃት ሊቀርብ እንደሚችል በገቢር ያሣየው ገጣሚ ፈቃዱ ጌታቸው፣ ይህ ትውልድ ከሃገሩ አልፎ ዓለምን የመሞገት ብቃት እንዳለው በአንድ የወግ ጽሁፉ ማሣመን የቻለው የ“ፋክት” መጽሔቱ አምደኛ ሚካኤል ዲኖ እና በተለያዩ መድረኮች ዝናን ያተረፉት የ“ፋቡላ ኪነጥበብ” አባላት የራስ ሆቴልን አዳራሽ በሀበሻ የጥበብ አየር ሞልተውት አምሽተዋል፡፡ የታዳሚውን ስሜትና የመንፈሥ እርካታ እንዲህ ነው ማለት ይከብደኛል፤ የአጋነንኩ ይመስልብኛልና! እራስዎት ጠይቀው ቢያረጋግጡ ይሻላል፡፡ አዘጋጆቹ፣ የ“ጦቢያ ግጥም በጃዝ” ቡድን አባላት ብራቮ!

Published in ጥበብ

ስግብግብነትን ጠንቁሎ ያወጣው ይመሥላል፡፡ ስግብግብነት ነገን የሚያይ ዓይን የለውም፡፡ ዛሬን ብቻ እያየ፣ ነገን የሚገድል ነቀርሣ ነው፡፡ ፀሐይን በሻማ ያሸጣል፡፡ ንፍሮ ለመቀቀል አጥር ያስፈርሳል፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ኤሣው ብኩርናን የሚያህል ታላቅ ክብር በምሥር ወጥ ይሸጣል፡፡ ዘመኑን ሁሉ በሆዱ አጭቆ ትውልድ ይገድላል! … ዮናስ በትንንሽ ነገሮች የተጠመደ ገጣሚ አይደለም፤ አይኖቹ ትልልቅ ክፍተቶችን አይተዋል፡፡ ሮበርት ሂሊየር ስለ ግጥም እንደ ግጥም በሚጣፍጡ ሙዚቃዊ ቃላት የሚጽፉ ምርጥ የግጥም ባለሙያ ናቸው - ለኔ፡፡ ገለፃቸው፣ አተያያቸው፣ ኩርኮራቸው ሁሉ ይጣፍጠኛል፡፡ ታዲያ እሣቸው ግጥምን ገና በጽንሱ ነው የሚሥሉት፡፡ በአእምሮ ውስጥ ክንፍ አውጥቶ ሲዋኝ! የባህር መዋዠቅ፣ የልብ ትርታ፣ የሁለንታው አለም (ዩኒቨርስ) ዳንስ እንቅስቃሴን የገጣሚ ጆሮ ይሰማል፡፡ ያንኑ እንደገደል ማሚቱ ያስተጋባል። እናም በዓለም ውጥንቅጥ ግራ አጋቢነት የተምታታው የሰው ልጅ ሕይወት፣ ጥሞና አግኝቶ ከሚውለበለብበት ረገብ እንዲል ግጥም ጆሮውን ትጠቅሰዋለች፤ የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡ በርሳቸው አባባል ግጥም ለጆሮ እንጂ ለዓይን አይደለም፡፡ ምናልባትም አንድ ፀሐፊ እንደሚሉት፤ ጆሮ ቀለም ያጣጥማል ሣይሆን አይቀርም፤ የልባቸው ድምጽ፡፡ ሴኔት ይሁን ሌሪክ፣ ኤፒክ ይሁን ባላድ ሁሉም ግን የነፍስን ነገር የማውጠንጠን አቅም አላቸው - እንደየስሜታችን፣ እንደልባችን ቁሥልና ሕመም፤ ዜማና ምት! ስለግጥም ማንበብም አንዳንዴ ግጥም የማንበብን ያህል ባይጥም ኖሮ የት እንገባ ነበር? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ፈረንጆቹ ብቻ ሣይሆኑ አቶ ብርሃኑ ገበየሁም ስለግጥም የፃፈበትን ቋንቋ በጣም አደንቅለታለሁ፡፡ (ለምን የፈረንጁን መጽሐፍ ሃሳብ ያለ ፈቃድ ወሰደ የሚለው ቅር ቢለኝም) ታዲያ በእጄ የያዝኳትን መጽሐፍ አንብቤ እያጣጣምኩ ሳለ፣ የዮናስ አብረሃም “ሦስት ዓይን” የግጥም መጽሐፍ እጄ ገብታ አገላብጬ አየኋትና የራሴን ገዛሁ፡፡ ዮናስ አብረሃም ብዙዎቻችን በማንረሳው የሬዲዮ ፋና “ልብ ለልብ” የደብዳቤዎች ፕሮግራም ላይ ከእማዋይሽ ዘውዱ ጋር ሲተርክ ነበር የማውቀው፡፡ ሁለቱም የማይረሣ ትዝታ አላቸው፡፡ “ትንንሽ ፀሐዮች” በሚባል ድራማውም የብዙዎችን ቀልብ መማረክ ችሏል፡፡ ስለዚህ ልቤን ካስደነገጡት፣ ስሜቴን ብቻ ሳይሆን ሕሊናዬን ካከኩልኝ ግጥሞች ጥቂቱን ለማየት ፈለግሁ፡፡ ከገጽ 77 ጀምሬ እንደ አረብኛ ጽሑፍ ወደፊት እመጣለሁ፡፡ “የአስከሬን አበባ” የሚለው ርዕስ ብዙ ጊዜ የተለመደውን የሞተ ሰው ማድነቅ ጉዳይ የሚያነሳ መስሎኝ ነበር፤ ግን አይደለም፡፡ የዘመናችንን ዋነኛ ሕመም፣ አሠቃቂ ግፍ የሚተርክ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ብዙ ሺህ ጊዜ በዝርው ቢፃፍም እንደ አዲስ “እህ” ብዬ እንድሰማው አድርጐኛል፡፡ እንዲህ ይነበባል:- ስለኔ ስትጮህ… ቁስሌን ስታክልኝ ካንተ ጋር ለማበር ጽዋ እንጠጣ ብትል… ባዶ ቅሌን ይዤ ገባሁኝ ባንተ በር፡፡ ስለኔነው ብዬ ከፊት ተሰለፍኩኝ - ባቆምከው ማህበር በገዛ ፈቃዴ… ጉልበቴ ተልጦ ወገቤ እስኪሰበር በአፍህ ብትዳብሰኝ ምታነሳኝ መስሎኝ ወንበር ሆኜ ነበር፡፡ ጀርባዬ ላይ በቅለህ ገርጥቼ ከወዛህ ዛሬ እንኳን አስታውስኝ፤ በጌጠኛው ሆቴል… ሆድህን እያሻሸህ ሆዴን አታስብሰኝ፤ ላፕቶፕ ዘርግተህ ስለኔ ያፈሰስከው የአዞ እንባህ ጠበሰኝ ቁልቁል አድርገኸኝ ከሆንክ አሜከላ ግፍ እስኪያፈነዳህ በችግሬ ነግድ ስሜን ሸጠህ ብላ!! በግጥሙ ተራኪው ገፀ ባህሪ፤ አንድ ባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በስሙ የነገደበትን ያወራል፡፡ እርሱም ተሟጋች አገኘሁ፤ አዛኝ መጣልኝ ብሎ አብሮት ይሰለፋል፤ ከወደቀበት የሚያነሳው መስሎት፣ ራሱን ወንበር ለማድረግ አልሰሰተም ነበር፡፡ ግና ወንበሩን አላስታወሰውም፡፡ እንጀራ መጋገሪያ ያደረገውን ምጣድ ከልቡ ሠርዞታል፡፡ ተራኪው ገርጥቷል፣ የግብረ ሰናይ ልብስ ያጠለቀው ዋሾ ወዝቷል፡፡ ይሄኔ ዘወር ብሎ በጌጠኛ ሆቴል ውስጥ ላፕቶፑን ዘርግቶ ስለርሱ ያፈሰሰውን እንባ ይታዘብና ጦር ይመዛል ስንል “ግፍ ያፈነዳልሃል” ብሎ መጪውን ቀን ይጠብቃል፡፡ እኔ ግን ግፍ እስኪያፈነዳው ባይጠበቅ ሕግ ቢያፈነዳው ብዬ እመኛለሁ… ቁልቁል አድርገኸኝ ከሆንክ አሜከላ ግፍ እስኪያፈነዳህ በችግሬ ነግድ ስሜን ሸጠህ ብላ!! የሚለው ሃሳብና ስንኞች ከነዜማና ምታቸው ቆንጆ ናቸው፡፡ ሃሳቡ ግን ትንሽ ያቁነጠንጣል፤ ቀጠሮ ባያገኝ ያስመኛል፡፡ ብቻ ገጣሚው ጥሩ ነገር ቃኝቷል፡፡ ያሳረረን ነገር ኮርኩሮታል፡፡ “ሞኝ የዕለቱን” የሚለውም ግጥም ቁምነገሩም ምቱም ጣዕም አለው፡፡ ዳሩን ዘንግተነው መሀል ስንሻማ ፀሐይዋን አጥፍተን ስንሮጥ ለሻማ፤ ጃንጥላ ተማምነን ዋርካውን ገንድሰን ንፍሮ ለመቀቀል አጥሩን አፈራርሰን በግለኝነት ጦስ… ችግሮች ስር ሰደው - አንድ ላይ ካበሩ አጥር በሌለበት እንዳይጠፋን በሩ፡፡ ጥቂት ስንኞች ትልቅና ግዙፍ ሀሣብ ይዘዋል። ንፅፅሮቹም ከፍ ባለ አቅም ተቀምጠዋል። ሥዕላቸውም ደማቅ፣ ለዛቸው ጣፋጭ ነው። ምናልባትም የዘመናችን ጉድፎች ከምንላቸው -ስግብግብነትን ጠንቁሎ ያወጣው ይመሥላል፡፡ ስግብግብነት ነገን የሚያይ ዓይን የለውም፡፡ ዛሬን ብቻ እያየ፣ ነገን የሚገድል ነቀርሣ ነው፡፡ ፀሐይን በሻማ ያሸጣል፡፡ ንፍሮ ለመቀቀል አጥር ያስፈርሳል። እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ መሣው ብኩርናን የሚያህል ታላቅ ክብር በምሥር ወጥ ይሸጣል፡፡ ዘመኑን ሁሉ በሆዱ አጭቆ ትውልድ ይገድላል! … ዮናስ በትንንሽ ነገሮች የተጠመደ ገጣሚ አይደለም፤ አይኖቹ ትልልቅ ክፍተቶችን አይተዋል፡፡ ቀጣዩ ግጥም “የዛሬን-ዛሬ ልንገርህ” የሚል ርዕስ አለው፡፡ ይሁን እንጂ ርዕሱ ምነው “ወረት” የሚል በሆነ ብያለሁ፡፡ የስሜት መለዋወጥ ነው ወረት፡፡ አሁን ያየነው ፍም መልሶ አመድ ሲሆን! … ሣይቆይ የሚጠወልግ ቅጠል አይነት! እንዲህ ይላል ግጥሙ:- ፍቅራችን ከእቶን ቢግልም ለነገ ዋስትና የለንም ምናልባት አድሮ አይኖርም፡፡ አንደበታችን ቢስማማ በአንድ ዋንጫ ብንጠጣ እርግጠኞች አይደለንም ነገ ምን እንደሚመጣ፡፡ የነገ ነገ ስላለ የዛሬን ዛሬ ውሰደው አሁን “መልአክ” ነህ ያልኩህን “ሠይጣን ነህ” ብዬ ሳልክደው፡፡ ተራኪው ራሱን ጠርጥሯል፤ ራሱን ፈርቷል፤ “ማን ያውቃል!” እያለ ነው፡፡ ስለዚህ ቡራኬህን ውሰድልኝ ነው የሚለው፡፡ ግጥም የማይረግጠው አበባ፣ የማያደማው እሾህ የለም፡፡ ከሕይወት ቁና ላይ ጣፋጭና መራራውን ይነካል፡፡ ትናንትን ሣይዘነጋ ዛሬን ይተርካል፤ ነገንም ይተነብያል፡፡ እውነተኛ የግጥም አንባቢ ደግሞ የዘመኑን ግጥም ብቻ የሙጢኝ ማለት የለበትም፤ እንደሂሊየር እምነት፡፡ የትናንትን ግጥሞች ሃይልና ውበት ወይም እውነትና ውበት፣ የዘመኑንም እንዲሁ ማጣጣም ግዱ ነው፡፡ ምናልባትም ግጥም እንደዝርው ፅሁፎች በየዘመኑ ጣዕሙን የሚጥል ሣይሆን፣ የዘመንን አድማስ የሚሻገር መሆን አለበት ይላሉ -የግጥም ባለሙያዎች፡፡ የዮናስ ግጥሞችም ላይ ከወደ ጭራቸው የሚጐትቷቸው ድክመቶች መኖራቸውን አንክድም! ብዙ የዘርፉ ጠበብት እንደሚስማሙበት፤ የግጥም ቋንቋ አዘወትራዊው ፈንጠር ያለ፣ ከፍታ ያለው ማማ ቢሆን ደግ ነው፡፡ እናም “ሦስተኛው ዓይን” ፓ! የሚያሠኝ ገለፃ፤ የዘይቤዎች ዳንስና ፍካት አልታየበትም፡፡ ምቱና ዜማው ደስ ይላል፡፡ እውነት ለመናገር የገጣሚው አይኖች ትኩረትና ውበትም የበለጠ ነው፡፡ ግን የተሻለ ሊፅፍ ይችላል፡፡ ወደ ሃሣብ ስንሄድ፣ ሀሣቦቹ ባብዛኛው የተመረጡ ቢሆኑም ክሊሼ የሆኑ ለዓመታት የተወራባቸው ሣይቀሩ መፅሐፍ ውስጥ ተካትተዋል። እነዚህ ደግሞ የመፅሀፉን ክብር በአፍጢሙ እንዳይደፉት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ቀዳሚ ምሣሌ የሚሆነን “የግድግዳው ሰዓት” የሚለው ነው። እናንብበው:- የግድግዳው ሰዓት … ከቆመ ቆይቷል፤ ምናልባት ጌጥ እንጂ … ጊዜ ማብሰር ትቷል አይተነው ባናምነው … “እውነት የለjትም ዋሽቷል” ያለው ማነው? ጨልሞ እስኪነጋ ነግቶ እስኪጨልም ሁለቴ ልክ ነው፡፡ ገጣሚው ይህንን ተብሎ ተብሎ የቸከ ሀሣብ ባይደግመው ይመረጥ ነበር፡፡ “አዝማሪው” የሚለው ግጥም ደግሞ፣ የዜማ ልፍስፍስነትና ስብራት ይታይበታል፡፡ ሙዚቃው ሞቷል፡፡ ደግሶ ሲጠራ… መብዛቱ ሲገርመኝ - አጓጉል አመስጋኝ የመሸታው ልክፍት … ኪነጥበብ መንደር “ዳር ዳር” ሲል አሰጋኝ፡፡ ግጥሙ ለአይን መምታቱ ብቻ የታየ ይመሥላል። ግና ደካማ ነው፡፡ “የሰይጣን ደግነት” የሚለው ግጥም ከ “የአስከሬን አበባ” ጋር መዝጊያው ይመሣሠላል፡፡ ተደጋጋሚ ሀሣብ ባይነሳ ይመረጣል። ይሁንና የዮናስ “ሦስተኛው ዓይን” እውነትና ውበት የተሞላ፣ አይን የሚስብ፣ ልብ የሚሰጠው መድበል ነው፡፡ አንድ ገጣሚ ግጥሞቹ ሁሉ ጥሩ እንዲሆኑ አይጠበቅም … የቱም ታላቅ ገጣሚ ዝርክርክ ግጥም ሾልኮ ይገባበታል፡፡ ብዙ ጊዜ ምርጫው ላይ ገለልተኛ አርታኢ ከጐን ሆኖ ቢያግዝ ጥሩ ነው፡፡ የዮናስ ቀጣይ የሳቁና የመጠቁ እንደሚሆኑ ብሩህ ተስፋ አለኝ፡፡

Published in ጥበብ

በሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው የፊልም ፌስቲቫልና የፊልም ውድድር ባለፈው ሳምንት

ተካሂዶ አሸናፊዎች ተሸለሙ፡፡
ድርጅቱ ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ባካሄደው ዝግጅት ፊልሞችን በእስር ዘርፎች አወዳድሯል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝምና ከደራሲያን ማህበር የተውጣጡ አምስት የፊልም ባለሞያዎች፣

ፊልሞቹን በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች በመመልከት ዳኝተዋል፡፡
ባለፈው ሰኞ በብሔራዊ ቲያትር በተከናወነው የመዝጊያና የሽልማት ስነስርዓት ላይ ይፋ እንደተደረገው “ኒሻን” ፊልም

በሶስት ዘርፎች አሸናፊ ለመሆን በቅቷል - በዓመቱ ምርጥ ፊልም፣ ምርጥ ዳይሬክተርና ምርጥ ሲኒማቶግራፊ፡፡



በወርሃ ታህሣሥ፣ 2001 ዓ.ም ነው … አንዲት ቀይ የቤት መኪና፣ ስድስት ኪሎ ከሚገኘው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

ዋናው ግቢ፣ በአንደኛ በር በኩል ወጥታ ቁልቁል ወደ አራት ኪሎ አቅጣጫ ከነፈች፡፡ የጣሊያኖችን የግፍ ጭፍጨፋ

ከሚዘክረው ሀውልት ጋ ሥትደርስ፣ ወደ ማርቆሥ ቤተክርሥቲያን ታጠፈችና አሁንም ቁልቁል ወደ አፍንጮ በር

ተተኮሰች፡፡ ሰዓቱ፣ 11፡45 አካባቢ እንደነበረ አሥታውሣለሁ፡፡ ቀዩዋ መኪና፣ የዩኒቨርሲቲው አንድ አንጋፋ መምህር

እያሽከረከሯት ወደ ፒያሳ አመራች፤ የመምህሩን አምስት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ብትጭንም፣ ከ12፡30 በፊት፣

አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴዝ ግቢ የማድረስ ሀላፊነት ተጥሎባታል፡፡ ቀይዋ መኪና ከተቆረጠው ሰዓት በፊት ጥቂት

ደቂቃዎችን ቀድማ ከተባለው ቦታ አደረሠችን፡፡
የአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴዝ ግቢ፣ ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በወጡ ሙዚቀኞች እንደተቋቋመ በተነገረለት “ሃራ

ሳውንድ ባንድ” አማካኝነት፣ ሞቅ ደመቅ ብሎ ይታያል፡፡ በመሣሪያዎች ብቻ የተቀናበሩ ጣዕመ ዜማዎች ይንቆረቆራሉ፡፡

ውጭ ላይ የተሠናዳው መድረክ፣ በህዝበ አዳም ተሞሽሯል፡፡ አሁን ጨለማው ዐይን ያዝ ከማድረግ አልፏል፤ ትላልቅ

ፓውዛ መብራቶች መድረኩን በብርሃን አድምቀውታል፡፡ የሙዚቃ ቅንብሩ በስፋት መደመጥ ያዘ፡፡ አንድ ገጣሚ መድረኩ

ላይ ወጥቶ በመሣሪያ ቅንብር ከሚወጣው ጣዕመ ዜማ ጋር በወጉ ተለክቶ የተሠፋ የሚመሥል የሰውነት እንቅስቃሴ

ማሣየት ጀመረ፡፡ የውዝዋዜው ሥልት፣ ከሙዚቃው ምት ጋር በእርጋታ እየተዋሀደ ከለብታ ወደ ሞቅታ ሲዛወር፣

የገጣሚው አንደበት ተከፈተ፡፡
ከዚያ ሥልጡን አንደበት ውስጥ የሚወጡ የተመጠኑ የስንኝ ቋጠሮዎች፣ በተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ምጣኔ ዜማ

ታጅበው ሲለቀቁ፣ በታላቅ ኪናዊ የመንፈስ ከፍታ ወደ ሰማየ ሰማያት የሚያርጉ ይመስሉ ነበረ፡፡ እኔ በበኩሌ ግጥም፣

ከዋሽንት ባለፈ በተለያዩ ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ቅንብር ታጅቦ ሲቀርብ ሣይ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ በመድረኩ ላይ

የተለያዩ ወጣት ገጣሚያን፣ ከሙዚቃው ምት ጋር የስንኞቻቸውን ምት እያዋደዱ በውዝዋዜ ሞሽረው ታዳሚውን

ማስኮምኮም ቀጥለዋል፡፡ መሀከል ላይ ይመስለኛል፣ የቀዩዋ መኪና አሽከርካሪ፣ አንጋፋው የዩኒቨርሲቲ መምህርም

መድረኩን ተቆጣጠሩት፤ ገጣሚው ፕሮፌሰር፣ ከወጣቶቹ ባልተናነሰ፣ እንደውም ካንዳንዶቹ በተሻለ ቆሞ ሲያሥተምር

የዋለ ወገባቸውን ከሙዚቃው ሥልት ጋር አዋደው ማወዛወዝ ጀመሩ፡፡ ግጥማቸውንም ከሙዚቃው ሥልት ጋር እያዋሀዱ

አቀነቀኑት፡፡ ይህ ቀን፣ በኢትዮጵያ የሥነ ጽሁፍ ታሪክ፣ ሥርዓት ባለው መልኩ ግጥም በጃዝ የቀረበበት ዕለት ተብሎ

ሊመዘገብ ይችላል፡፡
የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እንደማስታውሰው ከሆነ፣ በዕለቱ ግጥሙን በመሣሪያዎቹ ቅንብር ጣዕመ ዜማና በራሡ ሥልታዊ

ውዝዋዜ አጅቦ በማቅረብ መድረኩን የሟሸው ገጣሚ አበባው መላኩ ይመስለኛል፡፡ “ይመስለኛል”ን ያመጣሁት፣

የመጀመሪያው የመድረክ አሟሺ አበባው ነው ወይስ ደምሰው መርሻ? ባለ “አሻራ”ዋ ምሥራቅ ተረፈ ናት ወይስ ሰዓሊዋ

ምህረት ከበደ? ወይስ ደግሞ “ለግጥም ጥም ጠብታ” የበቃው ፍሬዘር አድማሱ? የሚለውን ቀዳሚ ሰው በውል ማስታወስ

ባለመቻሌ ነው፡፡ “እየሄድኩ አልሄድኩም” የሚሉት የቀዩዋ መኪና አሽከርካሪ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ግን መሀከል ላይ

ማቅረባቸው፣ ብዙ ጥርጣሬ አልፈጠረብኝም። ለማንኛውም ግን፣ ስድስቱ ገጣምያን የዕለቱ ባለ ታሪኮች እንደነበሩ

ለመጠቆም መፈለጌን ብታውቁልኝ አልጠላም፡፡
በርግጥ፣ ግጥም በጃዝ ሥርዓት ባለው ቡድናዊ አደረጃጀት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው በ2001 ዓ.ም ነው ቢባልም፣ ለዚህ

የቡድን ዝግጅት ከመብቃቱ በፊት ሌሎች ሙከራዎች እንደነበሩ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እስከ አሁን በተገኙ

ማስረጃዎች መሰረት፣ በ2000 ዓ.ም በብሔራዊ ትያትር አበባው መላኩ “ቅናት” የተሠኘ ግጥሙን በሲዲ በቀረበ የሙዚቃ

ቅንብር አጃቢነት ለተመልካች ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዕለት ከታዳሚው ከፍተኛ አድናቆት እንደተቸረው ተነግሯል፡፡

አበባው፣ በብሔራዊ ትያትር መድረክ ግጥሙን ከተቀናበረ ሙዚቃ ጋር ያቀርብ ዘንድ ንቃትና ብርታት የሆነው “ደግ

አይበረክትም” የተሠኘው የግጥም ሲዲው ዝግጅት ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡
እንግዲህ፣ ግጥምን በጃዝ መድረክ የሚያቀርበው የቡድን አባላት በአሊያንሥ ኢትዮ-ፍራንሴዝ ዝግጅትና በኋላም

በተለያዩ መድረኮች ግጥም በጃዝ ማቅረቡን እየሠለጠነበት መጣ፡፡ ቡድኑ፣ ከታዋቂው የፒያኖ ተጫዋች ግርማ ይፍራሸዋ

ጋር በጣሊያን የባህል ማዕከል ያቀረበው ዝግጅት፣ የወደፊቱን የከፍታ ዘመን አመላካች ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ በቦሌ

ሮክና በሸራተን አዲስ መድረኮች ላይም ኢትዮጵያዊ ግጥም በጃዝ ተሞሽሮ ይቀርብ ዘንድ የቡድኑ የላቀ ትጋትና ጥረት

ቀጠለ፡፡ በ2003 ዓ.ም፣ ወር በገባ የመጀመሪያው እሮብ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል መድረክ ላይ ከመለከት ባንድ ጋር በኋላም

ከአቢሲኒያ ባንድ ጋር በመተባበር ግጥም በጃዝ እየሸመኑ ማቅረብ ተወዳጅ ኪነት እየሆነ መጣ። የዋቢ ሸበሌው የአንድ

ዓመት የግጥም በጃዝ ጉዞ ሲስተናበር የነበረው በቸርነት ወልደ ገብርኤል፣ በደምሰው መርሻና በአበባው መላኩ እንደነበረ

ያሠባሠብኳቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚሁ ዓመት ወደ ኋላ ላይ ግሩም ዘነበና ሜሮን ጌትነት የቡድን አባላቱን

እንደተቀላቀሉ ሰምቻለሁ፡፡
አሁንም የግጥም በጃዝ መድረኮች፤ የታዳሚን ቀልብ እየገዙ፣ የኪነት ልክፍት ያለበትን እያፈዘዙ፣ የገነገኑ ሀገራዊ

ሰንከፎችን እየመዘዙ የስኬት ጉዟቸውን ተያያዙት፡፡ በ2004 ዓ.ም፣ ግጥም በጃዝ በራስ ሆቴል መድረኮች ላይ አብቦ

ይፈካ ዘንድ ጊዜው ፈቀደ፡፡ ወር በገባ የመጀመሪያው እሮብ የራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ፣ በታዳሚዎች መጣበብ ጀመረ።

የሆቴሉ ሰፊ ግቢ ሊሸከመውና ሊያስተናግደው ከሚችለው በላይ በሆኑ ረዣዥም ሰልፎች ይፈተን ዘንድ ግድ አለው፡፡

አዳራሹ፣ ከ800 በላይ የሚሆኑ ታዳሚዎች ጢም ብለው ሞልተው ይፈሡበታል፡፡ የሚገርመው ግን ይህ ሁሉ ታዳሚ

የሚርመሰመሰው ዝግጅቱ የሚቀርበው በነፃ ሥለሆነ እንዳይመሥልዎ! 50 ብር የመግቢያ ዋጋ ለመክፈል የተሠለፉ

የግጥም በጃዝ እድምተኞች፣ አዳራሹ እየሞላባቸው ሲመለሱ ማየት የየዕለቱ ክሥተት ሆኗል፡፡
የራስ ሆቴሉ ግጥምን በጃዝ መድረክ አሠናጂ የቡድን አባላት፣ ለግዜው “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” በሚል ሥያሜ፣ ድርጅት

ከፍቶ የኢትዮጵያን ግጥም በጃዝ አፍክቶ ማቅረቡን ተያይዞታል፡፡ በራስ ሆቴል መድረክ ወር በገባ በመጀመሪያው ዕለተ

እሮብ፣ ለጥበብ ሱሰኞች ምሣቸውን እያደረሠ ይገኛል። የቡድኑ የጥበብ ጉዞ ሥርዓት ባለው መንገድ እየተጓዘ፣

ለተከታታይ 28 ወሮች በመድረክ ላይ ነግሷል፡፡ ቡድኑ፣ ዝግጅቱን በተከታታይ ማቅረብ የጀመረበትን ሁለተኛ ዓመትም

ለማክበር በቅቷል፤ በዚሁ በዓል ላይ፣ የተመረጡ ዝግጅቶች፣ “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” (ቅጽ አንድ) በሚል ስያሜ በዲቪዲ

አሣትሞ በ50 ብር ዋጋ ለጥበብ ወዳጆች ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ በነገራችን ላይ በራስ ሆቴል መድረክ በጃዝ የሙዚቃ

ቅንብር ተከሽነው የሚቀርቡት ግጥሞች ብቻ አይደሉም፤ ስሜት ኮርኳሪ፣ መሣጭና እውቀት አጋሪ የሆኑ ወጐችና

ዲስኩሮችም ሢቀርቡ አይቻለሁ፡፡ እንደውም፣ በጦቢያ ግጥምን በጃዝ ቢሮ ውስጥ በተገኘ መርሐ ግብር መሠረት፣

በየዕለት መድረኩ 5 ገጣምያን፣ 1 ወግ ተራኪ እና1 ዲስኩር አቅራቢ የኪነት ቤተኞች ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ

ይታወቃል፡፡
የዛሬ የጦቢያ ግጥም በጃዝ ቡድን ተጠሪዎች፤ አበባው መላኩ፣ ምሥራቅ ተፈራ፣ ደምሰው መርሻ፣ ምህረት ከበደ፣ ግሩም

ዘነበና ሜሮን ጌትነት ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ፣ በዘመነኛ ትንታግ ገጣሚነታቸው ይታወቃሉ፤ በመካከላቸው በትወናም

የተጨበጨበላቸው ይገኛሉ፡፡ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ አብዛኞቹ የቡድን አባላት በተለያዩ መድረኮች በግጥም

ተናግረዋል፤ ለግጥም ተዋድቀዋል፤ ስለ ግጥም አንብተዋል፤ ስለ ግጥም ቆመዋል፤ ለግጥም ጦም አድረዋል፡፡ ዛሬ ግን

በግጥም እያሠቡ፣ በግጥም ትውልድ ይሞግታሉ፤ በግጥም ተከብረው፣ በግጥም በልተው አድረዋል፡፡
ዛሬ ይህ ቡድን፣ ከተለያዩ ኤምባሲዎችና ከተለያዩ ድርጅቶች የአብረን እንስራ ጥሪ ይቀርብለታል። በታወቁ ተቋማት

ስፖንሰርነት፣ የተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮችን ይወጣ ይዟል፡፡ ለምሣሌ በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም፣ ከያኒው ሰርክ

የሚጠበብበት ተፈጥሮ፣ ህልውናዋ አደጋ ላይ መውደቁን ለማጠየቅ፣ በብሔራዊ ትያትር መድረክ “ጥበብ ለተፈጥሮ”

በሚል ርዕስ የተደነቀ ዝግጅት አቅርቧል፤ በዕለቱ የቀረቡት ግጥሞች በ80 የፖሊስ የማርሽ ባንድ አባላት ታጅበው

እንደነበረ ይታወሣል፡፡
ዛሬ፣ “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” የቡድን አባላት፣ የራስ ሆቴልን መድረክ በጥበብ አድምቀው የሚሞሸሩት፣ በራሣቸው

“የመንፈስ ከፍታ” ያህል ብቻ በመንጠቅ አይደለም፤ የተለያዩ ገጣሚዎችን፣ ወግ አራቂዎችን፣ ዲስኩር አቅራቢዎችን ወዘተ

በመጋበዝ አዳዲስ ጥበበ ቃላት እንዲከሸኑ ሥርዓት ዘርግተዋል እንጂ፡፡ ለዚህ ነው፣ ከእግረ ተከል የኪነት ባለሟሎች

እስከ ጉምቱ የጥበብ አያቶች ድረስ በመድረክ ላይ ሢዘምኑ የሚታየው፤ በእውነትና በእውቀት እየተመሙ፣ ኪናዊ ውበት

ሲያፈልቁ የሚገኘው፡፡
ዛሬ ግጥም በጃዝ መድረክ የሚደነቅና የሚወደድ ውበት ብቻ ሣይሆን የሚናፈቅ ሕይወትም እየሆነ ያለ ይመሥላል፡፡

ዛሬ፣ 50 ብር ከፍለው የሚታደሙ አድናቂዎች ብቻ አይደለም የሞሉት፤ የዓመታት ወጪ ሸፍነው የቡድኑ አባል ለመሆኑ

የሚታትሩ ጭምር ተመዝግበዋል እንጂ፡፡ ዛሬ ቡድኑ፣ ጥበብን የሚያቀርብበት የነፃ አዳራሽ መንግሥት ይፍቀድልኝ

አይልም፤ እንደውም በየወሩ ለመንግሥት በሺዎች የሚቆጠር ብር ይገብራል እንጂ፤ “ግብር አይደለም ዕዳ” እንዲል

የገቢዎች ሚኒስቴር፡፡
ምን አለፋዎት … ግጥም በጃዝ መድረክ ላይ በሃበሻ ግጥም፣ የሀበሻ እውነትና እውቀት በጥበባዊ ሥልት ተፈታትቶ

በምርጥ የቃላት ጡብ፣ ሢገጣጠም ያያሉ (እመኑኝ እያጋነንኩ አይደለም-በፍፁም)፡፡ ከሃበሻ የኑሮ ልማድ ውስጥ

እውነቱና እውቀቱ በብልሃት ይተነተናሉ-በግጥም፡፡ ከእውነቱና ከእውቀቱ የተጠነፈፈው ማንነቱ በቃላት ምታት መድረክ

ላይ ሢሠጣ፣ ታዳሚው እየሣቀ ይተክዛል፤ እያጨበጨበ ይቆዝማል፡፡ ግጥሞቹ፣ ወጉና ዲስኩሩ በሀበሻ የመንፈስ ክር

የተሣሠሩ ሽንፈቶቹን፣ ቁጭቶቹን፣ ህልሞቹን ይናገራሉ፤ ከሀገር እውቀቶቹና እውነቶቹ ጋር እየተጣቀሡም፣ የዘመን

መንፈስን እያሥጠቀሡ፣ ገዝፈውና በዝተው ይቀነቀናሉ፡፡ የአዳሚም የታዳሚም መንፈስ ከፍ ብሎ ይንሣፈፋል፤ ዝቅ

ብሎም ይነፍሣል … እኔ በበኩሌ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነትም በተማሪነትም ያጣሁትን የመንፈሥ ልዕልና በዚያ

አዳራሽ ውስጥ የተጐናፀፍኩ አይነት ነው የሚሠማኝ፡፡ የሀበሻ ግጥም፣ ወግና ዲስኩር በተቀናበረ ሙዚቃ ታጅበው

እውነት፣ እውቀትና ውበት በሚያፈልቁበት በዚህ አዳራሽ፣ የሰዓታት ሰላም ያገኘሁ ይመሥለኛል፡፡
እስኪ በራሥ ሆቴል አዳራሸ ከሚቀርቡ ዝግጅቶች መካከል የቅርቡን (ህዳር 4 ቀን 2006 ዓ.ም) የጥበብ ድግሥ

በጨረፍታ ልጠቁማችሁ። እንደተለመደው ትልቁ አዳራሽ ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሏል፡፡ የውጭ ሀገር የመገናኛ

ብዙኃን ባልደረቦች ትላልቅ መቅረፀ ምሥል ካሜራዎችን ተሸክመው ዝግጅቱን ለመቅረጽ ከወዲያ ወዲህ ሽር ጉድ

ይላሉ፡፡ “ነፃ አውጪ ባንድ” በመሣሪያ የተቀነባበሩ ጣዕመ ዜማዎችን ያሠማሉ፡፡ የመድረክ አጋፋሪው፣ ዝነኛው ተዋናይ

ግሩም ዘነበ ወደ መድረኩ ጐራ እያለ በአስገምጋሚ ድምፁ መርሐግብሩን ያሥተዋውቃል፡፡
በዚህ ዕለት፣ የሸገር ሬዲዮ ባልደረባው ስመ ጥሩ የመድረክ ሰው ተፈሪ ዓለሙ፣ የሁለት ትውልዶችን ብጭቅጫቂ ኑሮ በ

“ስውር-ስፌት” እየጠቀመ ያለው (“ጠ” ጠብቃ ትነበብ) የአዲስ አድማሱ ዋና አዘጋጅ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ ሢያሻው

በግጥም መናገር የሚችለው ታዋቂው ሰዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን፣ የዕለቱን መድረክ “የመንፈስ ከፍታ” አግዝፎ የናኘው

ገጣሚ በረከት በላይነህ፣ ለግጥም ወይም ስለ ግጥም ሕይወተን እየከፈለ ያለ የሚመሥለኝ ገጣሚ ደምሰው መርሻ፣ መሪር

ሰዋዊ ግዙፍ ጥያቄዎች በተራኪ ግጥም እንዴት በብልሃት ሊቀርብ እንደሚችል በገቢር ያሣየው ገጣሚ ፈቃዱ ጌታቸው፣

ይህ ትውልድ ከሃገሩ አልፎ ዓለምን የመሞገት ብቃት እንዳለው በአንድ የወግ ጽሁፉ ማሣመን የቻለው የ“ፋክት”

መጽሔቱ አምደኛ ሚካኤል ዲኖ እና በተለያዩ መድረኮች ዝናን ያተረፉት የ“ፋቡላ ኪነጥበብ” አባላት የራስ ሆቴልን

አዳራሽ በሀበሻ የጥበብ አየር ሞልተውት አምሽተዋል፡፡ የታዳሚውን ስሜትና የመንፈሥ እርካታ እንዲህ ነው ማለት

ይከብደኛል፤ የአጋነንኩ ይመስልብኛልና! እራስዎት ጠይቀው ቢያረጋግጡ ይሻላል፡፡ አዘጋጆቹ፣ የ“ጦቢያ ግጥም በጃዝ”

ቡድን አባላት ብራቮ!

Published in ጥበብ

በወጣትና አንጋፋ ከያንያን በየወሩ የሚቀርበው “ግጥም በጃዝ” 29ኛ ዝግጅቱን የፊታችን ረቡዕ ከምሽቱ 11፡30 ጀምሮ በራስ ሆቴል አዳራሽ እንደሚያቀርብ አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ በምሽቱ የጥበብ ዝግጅት ላይ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን፣ አበባው መላኩ፣ ሜሮን ጌትነትና ገዛኸኝ ፀጋው ግጥም ሲያቀርቡ፤ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወግ፣ በኃይሉ ገብረመድሕን ደግሞ ዲስኩር ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ የዝግጅቱ መግቢያ በነፍስ ወከፍ 50 ብር ነው፡፡

በሻሸመኔ ከተማና አቅራቢያዋ ኪነጥበብ አፍቃሪዎች የተቋቋመው “ከአድማስ ፊት” የኪነጥበብ ማህበር 45ኛ ዝግጅቱን ነገ ከቀኑ 7 ሰአት በሻሸመኔ የባህል አዳራሽ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ በ “ትናንሽ ፀሐዮች” እማ ጨቤን ሆና የምትተውነው አርቲስት ሰብለ ተፈራ ነች። በነገው ዝግጅት የጭውውት፣ የግጥም፣ የዘፈን፣ የመነባንብ ሥራዎች ይቀርባሉ፡፡ ማሕበሩ ካሁን በኋላ በየወሩ በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ውድድር እያካሄደ ለአሸናፊዎች የሚሸልም ሲሆን የነገው ውድድርም በኮሜዲ ዘርፍ እንደሚሆን ማሕበሩ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ከ“አድማስ ፊት” የተመሰረተበትን 6ኛ ዓመት በ50ኛ ዝግጅቱ በመጪው ሰኔ ለማክበር እየተዘጋጀ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

Page 13 of 16