ስመ ገናናው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ባለፈው ሳምንት 100ኛ የሙት ዓመታቸው ተከብሮላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ 20ኛው ክፍለዘመን እንድትሻገር ፈሩን በመቅደድ  ዘላለም ታሪክ የሚያስታውሳቸው ንጉሥ ናቸው። ሳህለ ማርያም በሚለው ክርስትና ስማቸው የሚታወቁት አፄ ምኒልክ፤ ኢትዮጵያን ለ24 ዓመታት በንጉሠ ነገሥትነት ያስተዳደሩ ሲሆን ዙፋናቸውን የለቀቁት በ69 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ  በንግሥና ዘመናቸው የጣሊያን ወራሪን በአድዋ ጦርነት አሸንፈው ከአገር በማስወጣት፣ ለመላው አፍሪካ እና ቅኝ የተያዙ አገራት ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት በመሆን በዓለም እውቅና አግኝተዋል፡፡ ከአድዋ በኋላ ደግሞ  ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ስልጣኔ በሯን እንድትከፍት አድርገው ብዙ አዳዲስ ነገሮችን አስጀምረዋል። ይህን ሃሳባቸው ለመፈፀም ሲሞክሩ፤ ”ፈረንጆች ሃገራችን ከገቡ ባህላችን ይለወጣል፤ ሃይማኖታችን ይጠፋል፤ ወኔያችን ይሰለባል” በሚሉ ተቃውሞዎች ከፍተኛ ፈተና ተጋፍጠዋል፡፡ የእምዬ ምኒልክን  100ኛ ሙት ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ከታሪክ መጻሕፍት እና ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በማጣቀስ  እንዲህ ይዘከራሉ፡-
“አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚል ርዕስ በተክለ ጻዲቅ መኩርያ በተዘጋጀው መጽሐፍ፤ በ1888 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ፣ ንጉሡ የጣሊያንን ወረራ በቅርብ አረጋግጠው፣ ለአድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ በይፋ ነጋሪት ያወጁት  የሚከተለውን መልዕክት በማስተላለፍ ነበር፡- ‹‹እግዚአብሄር በቸርነቱ  እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡  ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም…›› ብለዋል፡፡ (ገፅ 226)
አፄ ምኒልክ ከውጭው ዓለም ጋር በርካታ የዲፕሎማሲ ፈር ቀዳጅ ተግባራትንም በማከናወን ይታወቃሉ፡፡ በ1893 እ.ኤ.አ የሩስያ የዲፕሎማቲክ እና የጦር ሚስዮን ልፁካን ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ነው የዲፕሎማሲ ጥረቱ የተጀመረው፡፡ በአድዋ ጦርነት ማግስት ራሽያ ብቻ ሳትሆን በርካታ የውጭ አገር ዜጎች፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለንግድ፣ ለግብርና፣ ለማዕድን ቁፈራ እና ሌሎች የሚሲዮን ተግባራት ወደ ኢትዮጵያ በብዛት መግባት ያዙ፡፡ ከአድዋ ጦርነትና ድል በኋላ በጠንካራ መሰረት በተጀመረው የኢትዮጵያ እና የራሽያ ዲፕሎማሲ ግንኙነት መነሻነት እስከ 1913 እ.ኤ.አ በሺዎች የሚገመቱ መኳንንቶች እና ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን በራሽያ ስፖንሰርነት ወደዚያው አገር በመሄድ ከፍተኛ የልምድ ልውውጥ ማድረግ ችለዋል፡፡ ከአድዋ ጦርነት በኋላ የሩስያ ቀይ መስቀል ልዑካን አዲስ አበባ ሲገቡ፣ ከንጉሡ ባገኙት ትብብር የመጀመሪያውን ዘመናዊ ሆስፒታል መሥርተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ መዲና ለመሆን የበቃችውን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን በዘመናዊ መዋቅር የቆረቆሩት አፄ ምኒልክ፤ በኢትዮጵያ በርካታ አዳዲስ ጅማሮዎችን በመፍጠር ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ በግብፆች አስተዳዳሪነት “አቢሲኒያ ባንክ” በሚል ስያሜ የመጀመሪያውን ባንክ፤ የመጀመሪያውን ፖስታ ቤት “አራዳ ፖስታ”፤ በኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ትብብር የተሰራው የመጀመርያው  የባቡር መንገድ፣ የመጀመርያዎቹ የስልክና የቴሌግራፍ አገልግሎቶች፤ የመጀመርያው የሞተር መኪና፤ የመጀመርያው የውሃ ቧንቧ እንዲሁም በመንግሥት አስተዳደር የመጀመርያው የሚኒስትሮችን ካቢኔ አቋቁመዋል፡፡
በ1990ዎቹ መግቢያ ላይ አፄ ምኒልክ የሞት ቅጣት መፈፀሚያ የሆኑ 3 የኤሌክትሪክ ወንበሮች እንዲመጣላቸው አዝዘው እንደነበር ይነገራል፡፡ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጠገብ ያለች አንዲት ዛፍ፣ በሞት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው ሰዎች ይሰቀሉባት ነበር፡፡ ምኒልክ ያንን ፈረንጆቹ እንዳያዩ ለማድረግ ቢጥሩም አልቻሉም፡፡ ፈረንጆቹ በነሱ አገር የሞት ፍርድ በኤሌክትሪክ ወንበር እንደሚከናወን ነገሯቸው፡፡ ያን ጊዜ ነው ምኒልክ ወንበሮቹን እንዲያመጡላቸው ያዘዙት፡፡ ሆኖም ወንበሮቹ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ሥራ ላይ ሊውሉ አልቻሉም፡፡ በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል አልነበረም፡፡
አፄ ምኒልክ ጥረታቸው ዋጋ እንዳያጣ አስበው፣ የውጭ አገር ሰዎች ከአገራቸው የኤሌክትሪክ ሃይልና ብርሃን እንዲያስመጡ በማድረግ፣ ከሶስቱ የኤሌክትሪክ ወንበሮች አንዱን ለሊቀመኳሳቸው፣ ሌላውን ወደ ግምጃ ቤት አስገብተውታል፡፡ ወንበሩን ለራሳቸው የዙፋን መቀመጫ እንዳዋሉ በቀልድ መልክ የሚነገረውን እንደ እውነተኛ ታሪክ አድርገው የጻፉ ግን አልጠፉም፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በ1930ዎቹ ይሄን ጉዳይ የምኒልክ አስገራሚ ታሪክ አድርጐ የፃፈው አንድ ካናዳዊ ጋዜጠኛ ይጠቀሳል፡፡
ብስክሌት ከመንዳት ጋር በተያያዘ ሌላ አስገራሚ ታሪክም ለአፄ ምኒልክ ይነገርላቸዋል፡፡ ንጉሡ ባንድ ወቅት ዲፕሎማቶች እና መኳንንቶቻቸውን በቤተመንግስት ሰብስበው “ብስክሌት እነዳለሁ” ብለው ተነሱ፡፡ ብስክሌቷ ላይ ተፈናጥጠው  ሲሞክሩ ስድስት ጊዜ ወድቀው በመነሣት፣ በመጨረሻ ቢስክሌት መንዳት የቻሉ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆነዋል፡፡
አፄ ምኒልክ በዘመነ መንግሥታቸው አጋጥሞ ከነበረ የከፋ ድርቅ ጋር በተያያዘም ለአገራቸው ሕዝብ ያስተማሩት መልካም ነገር ነበር፡፡ በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ድርቅ፣ የአገሬው ሕዝብ ረሃብ ሲያሰቃየው፣ ንጉሡ ወደ እርሻ ማሳ ወጥተው፣ በዶማ መሬት በመቆፈር፣ ገበሬዎች የማረሻ በሬ ባይኖራቸው እንኳን በእጃቸው መሬት ቆፍረው ማብቀል እንደሚችሉ በተግባር በማሳየት አስተምረዋል፡፡ በዚሁ የድርቅ ወቅት ንጉሡ የግብር ምህረት በማድረግም ወገናቸውን ረድተዋል፡፡
አፄ ምኒልክ ከአድዋ ጦርነት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት በማስገባት የላቀ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የተክለ ጻዲቅ መኩርያ “አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” የተሰኘው የታሪክ መፅሃፍ፤ ወደ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት እንዴት እንደገባ ሲያብራራ፤
‹‹የካቶሊክ እምነት ካላቸው ፈረንሳዮች ፤ፀረ ማርያም ከሚባሉት ከእንግሊዞች መምህርነት በመፈለግ በአገር ውስጥ ጠብ እንኳን ቢቀር ማጉረምረም እንዳይፈጠር ሲሉ፣ የተዋህዶ ኃይማኖት ከመነጨበት፣ ጳጳስ ከሚመጣበት ከእስክንድርያ ወይም ከግብፅ አገር መምህራንን በገንዘብ ቀጥረው ማስመጣትን መረጡ…›› በዚህ መሰረትም በ1900 ዓ.ም የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤትን አቋቁመው፤ የመሳፍንት፣ የመኳንንት፣ የደሃ ልጆችም ቁጥራቸው 150 የሚደርስ ወጣቶች ተደባልቀው ይማሩ ዠመር። አፄ ምኒልክ ስለትምህርት መስፋፋት ያላቸውን የጋለ ምኞት ትምህርት ቤቱ ከመቋቋሙ  በፊት ያወጡት አዋጅ ያሳያል፡፡
“…እስካሁን ማንም የእጅ አዋቂ የነበረ ሰው በውርደት ስራ ይሰራ ነበር፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው ለመማር እና ለመሰልጠን የሚተጋ አልነበረም፡፡ በዚህ ጎጂ በሆነ ሁኔታ ብንኖር፤ ቤተክርስትያኖች ይዘጋሉ፡፡ ይልቁንም ክርስትያንም አይገኝም። በሌሎች አገር እያንዳንዱን ነገር  መማር ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ነገሮችም ይሰራሉ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ለወደፊት ወንድ ልጆች እና ሴት ልጆች ሁሉ ከስድስት ዓመታቸው በኋላ ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ይሁን፡፡ ልጆቻቸውን ለማስተማር ለማይተጉ ቤተሰቦች፣ ወላጆቻቸው ሲሞቱ ሃብታቸው የልጆቻቸው መሆኑ ቀርቶ ለመንግሥት ይተላለፋል፡፡ ተማሪ ቤቶች እና አስተማሪዎችን የሚያዘጋጀው መንግሥት ነው፡፡››
በአፄ ምኒልክ ጊዜ ሕዝቡ በሸቀጣሸቀጥ፣ በምርትና በአሞሌ ጨው ከመገበያየቱ በቀር ለከፍተኛ ዋጋ የሚጠቀመው ከመካከለኛው ምሥራቅ በ1768 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ በገባው የኦስትሪያ ንግሥት ማርያ ትሬዛ ምስል ያለበት ብር ነበር፡፡ በአክሡምና ከዚያ በፊት መገበያያ ገንዘቦች (ሳንቲሞች) የነበሩ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ተመልሶ ዕቃን በዕቃ መለዋወጥ ተጀመረ፡፡  አፄ ምኒልክ በዚህ ፀፀት ተሰምቷቸውኧ በ1894 እ.ኤ.አ ከፈረንሳይ ኩባንያ ጋር በመዋዋል፣ በመልካቸው እና በስማቸው (ብር ከእነ ቅንስናሹ)  20ሺ ብር አሳትመው በእሱ መገበያየት መጀመሩን የተክለፃድቅ መኩርያ መፅሃፍ ያወሳል፡፡ በፈረንሳዩ ኩባንያ በመጀመርያ የተሰራው አንድ ብር፤ የብር አላድ፤ የብር ሩብ፤ የብር ስምንተኛ ነበር። የብሩ ክብደት እስከ 28 ግራም ሲሆን ባንድ ወገኑ “ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” የሚል፣ “1889” በኢትዮጵያ አሃዝ የተጻፈበትና የራሳቸውን ዘውድ የደፋ ምስል የያዘ ነው፡፡ በግልባጩ ደግሞ ዘውድ የደፋና በቀኝ እጁ ባንዲራ ያለበት ባለመስቀል ሰንደቅ የጨበጠ አንበሳ ሆኖ፣ በዙርያው “ሞዓ አንበሳ እምነገደ ይሁዳ”፣ እንዲሁም አንድ ብር የሚለው ሰፍሮበታል፡፡ ይህ የምኒልክ አዲስ ገንዘብ ሕጋዊ መገበያያ እንዲሆን የተነገረው አዋጅ…
“ከዚህ ቀደም ነጋዴም፤ ወታደርም ባላገርም፤ የሆንክ ሰው ሁሉ በየገበያውና በየመንገዱ በየስፍራው ሁሉ በጥይት ስትገበያይ ትኖር ነበር። አሁን ግን በእኔ መልክ እና ምስል የተሰራ ብር፤ አላድ፤ሩብ፤ተሙን፤ መሃልቅ አድርጌልሃለሁና በዚህ ተገበያይ እንጅ ከእንግዲህ በጥይት መገበያየት ይቅር ብዬሃለሁ፡፡
ይህን አዋጅ አፍርሶ ጥይት እርስ በራሱ ሲሻሻጥ እና ሲገዛዛ የተገኘው… በአንዳንድ ጥይት አንዳንድ ብር ይክፈል..” የሚል ነበር፡፡
ታዋቂው የሙዚቃ ሰው አቶ ተስፋዬ ለማ፤ “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ” ብለው ባዘጋጁት ምርጥ መጽሐፍ፤ አፄ ምኒልክ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ እንዲስፋፋ በነበራቸው ፍላጎት እና በጣሉት መሰረት ስማቸው ተወስቷል፡፡ የአድዋ ድል አንደኛ አመት ሲከበር፣ በወቅቱ የራሽያ ንጉሥ  የነሐስ የሙዚቃ መሳርያዎችን፤ ኮሎኔል ሊኦንቴፍ ከተባለ አሰልጣኝ ጋር ለምኒልክ መላካቸውን የሚገልፀው “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ” የተባለው መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በምኒልክ ዘመን ዘመናዊ ሙዚቃ እንዴት አገር ውስጥ እንደገባ ሲተርክ፤ ‹‹ከሩስያ በመጡት የትንፋሽ መሳርያዎች ለመማርና ለመጫወት የፈቀደ አልነበረም፡፡ ኮሎኔል ሊኦንቴፍም በኢትዮጵያ ሙዚቃ የተናቀ ሙያ መሆኑ ገረመው፡፡ ….. በመጀመርያ ከቤኒሻንጉል እና ከወላይታ የተገኙ ሰዎች ተመልምለው የሙዚቃ መሳርያዎችን ለመጫወት ለሶስት ወራት ሰለጠኑ። አፄ ምኒልክ በተገኙበት አሰሙ፤ ተመስግነው ተሸለሙ፡፡›› ብሏል፡፡
የአፄ ምኒልክ አዝማሪ የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፤ ለመጀመርያ ጊዜ የአማርኛ ዘፈኖችን በርሊን ጀርመን ውስጥ በዲስክ አሳትመው ማሰራጨታቸውን ይሄው መፅሃፍ ከትቦታል፡፡

Published in ህብረተሰብ

በደቡብ አፍሪካ በሚስተናገደው 3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ (CHAN) የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን ከሳምንት በኋላ እንደሚጀምር ታወቀ፡፡  በቻን ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ የሚቀርበው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከምድብ ማጣርያው ማለፍ እንደሚችል ግምት ቢያገኝም በቂ ዝግጅት ሳይኖረውና ለአቋም መፈተሻ የሚሆን የወዳጅነት ጨዋታ  አለማድረጉ ተሳትፎውን ሊያከብድበት ይችላል፡፡ ዋልያዎቹ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ በቻን ውድድር  በማግኘት ትኩረት ይስባሉ፡፡ በአገር ውስጥ ክለቦች በሚገኙ ተጨዋቾች ስብስብ በሚዋቀረው ብሄራዊ ቡድኑ ላይ ወሳኝ ሚና ሊኖራቸው ከሚችሉ ተጨዋቾች መካከል  በሴካፋ የታዩ አዳዲስ ዋልያዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በ3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ በምድብ 3 ኢትዮጵያ ፤ ከጋና፤ ከሊቢያ እና ከኮንጎ ብራዛቪል ጋር መደልደሏ ይታወቃል፡፡ የመጀመርያ ጨዋታዋን ከሊቢያ ጋር፤ ሁለተኛ ግጥሚያዋን ከኮንጎ ብራዛቪል ጋር እንዲሁም የመጨረሻ ግጥሚያዋን ከጋና ጋር ታደርጋለች፡፡ ሁሉንም ጨዋታዎች የምታደርግበት ፍሪስቴት ስታድዬም 40911 ተመልካች የሚያስተናግድና በብሎምፎንቴን ከተማ የሚገኝ ነው፡፡ ፍሪስቴት ስታድዬም በ1996 እኤአ ላይ 7 የአፍሪካ ዋንጫ  ጨዋታዎችን፤ በ2009 እኤአ አራት የኮንፌደሬሽን ካፕ ካፕ ጨዋታዎችን እንዲሁም በ2010 እኤአ 6 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ያስተናገደ  ነው፡፡
ኮንጎ ብራዛቪል እና ኢትዮጵያ በቻን ውድድር የመጀመርያ  ጊዜ ተሳታፊ ናቸው፡፡ ጋና ለሶስተኛ ጊዜ ከመሳተፏም በላይ በ2009 እኤአ ለዋንጫ ተጫውታ ሁለተኛ ደረጃ ስታገኝ በ2011 እኤአ ደግሞ ከምድብ ማጣርያው ተሰናብታለች፡፡ ሊቢያ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ  በቻን የምትሳተፍ ይሆናል፡፡  
ኢትዮጵያ የምድብ ማጣርያውን አልፋ ወደ ሩብ ፍፃሜ ከገባች በጥሎ ማለፍ ልትገናኝ የምትችለው በምድብ 4  ከሚገኙት ከኮንጎ ዲ ሪፖብሊክ፣ ጋቦን፣ ብሩንዲ ወይም ሞውሪታንያ ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምድብ 3 አንደኛ ከሆነች በምድብ 4 ሁለተኛ ሆና ከጨረሰው ጋር በኬፕታውን ከተማ በሚገኘው የኬፕታውን ስታድዬም ወይም ደግሞ በምድብ 3 ሁለተኛ ከሆነች ከምድብ 4  አንደኛ ጋር በፖልክዋኔ ከተማ  በሚገኘው ፒተር ሞካባ ስታድዬም  በጥሎ ማለፉ ትገናኛለች፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በአንድ ምድብ ለሚገኘው የጋና ቡድን 28 ተጨዋቾች ከአገሪቱ ስኬታማ ክለቦች ተመርጠውበት ባለፈው ማክሰኞ ዝግጅቱን በአክራ ጀምሯል፡፡ ይህ የጋና  ቡድን  በነገው እለት ለአቋም መፈተሻ እንዲሆነው በአክራ የማሊን ብሄራዊ ቡድን ያስተናግዳል፡፡ ከዚህ ጨዋታው በኋላ የመጨረሻ ዝግጅቱን ለማድረግ በሚቀጥለው ሰኞ  ወደ ናሚቢያ እንደሚያቀና ሲታወቅ ከውድድሩ መጀመር በፊት ከናሚቢያም ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በሱዳን በተደረገው 2ኛው የቻን ውድድር የጋና ቡድን ከምድብ ማጣርያው የተሰናበተበትን ደካማ ውጤት ዘንድሮ እስከ ዋንጫው በመገስገስ ለማሻሻል ታስቧል፡፡ የጋና ቡድን በምድቡ የተሻለ ግምት በመስጠት የሚጠባበቀው የኢትዮጵያ ቡድንን እንደሆነ እየተገለፀ ሲሆን የምድብ ድልድሉ በወጣበት ወቅት በስፍራው የነበሩት የሊቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ከምድብ 3 የምናልፈው እኛ እና ዋልያዎቹ ነን ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል በቻን ውድድር የናይጄርያ ቢ ቡድንን ይዞ እንደሚቀርብ ያስታወቀው ስቴፈን ኬሺ ዋንጫውን ማሸነፍ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል፡፡ በምድብ 1 ከአዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ፤ ማሊ፤ እና ሞዛምቢክ ጋር የተመደበው የናይጄርያ  ቡድን ለቻን ያደረገው ዝግጅት በቂ እንዳልሆነ የተናገረው ስቴፈን ኬሺ ለአቋም መፈተሻ የሚሆነው ግጥሚያ አለማድረጉ በብቃት ላይ ተፅእኖ መፍጠሩ አይቀርም ብሏል፡፡ የናይጄርያ ቢ ቡድን በቀን ሁለቴ ልምምድ እየሰራ የቻን ውድድርን ይጠባበቃል፡፡ የቻን ውድድር ለዋናው ብሄራዊ ቡድን በብቃት ተተኪ የሚሆኑ ተጨዋቾችን ለማግኘት ያስችላል ያሉት ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት ይዘው የሚቀርቡት ጎርደን ሌጀሰንድ ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ የቻን ውድድርን በማዘጋጀቷ ብሄራዊ ቡድኑ በውድድሩ እስከመጨረሻው ምእራፍ ሊጓዝ የሚችልበትን ድጋፍ ያስገኝለታል ያሉት ጎርደን ሌጀሰንድ ዋንጫውን የማሸነፍ ፍላጎት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆነው ሰርዴዮቪች ሚሉቲን ለቻን ውድድር ቡድኑን በወጣትነት እና ልምድ ባላቸው ተጨዋቾች በመገንባት እንደሚቀርብ ተናግሯል፡፡ ዘ ክሬንስ የተባለው የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን በቻን ውድድር በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የሚሳተፍ ሲሆን ያሉበት ምድብ ጠንካራ ቢሆንም ወደ ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ለመግባት ከፍተኛ ትግል እናደርጋለን ብለዋል፡፡ በ3ኛው የአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ ላይ ያሉት አራት ምድቦች ድልድል ማን የበላይ እንደሚሆን ለመገመት የሚያስቸግር ነው የሚለው ሚቾ ኡጋንዳን እስከ ሩብ ፍፃሜ ለማድረስ እቅድ እንዳለው አመልክቷል፡፡ ኡጋንዳ በምድብ 2 ከዚምባቡዌ ፤ ከቡርኪናፋሶ እና ከሞሮኮ  ጋር መመደቧ የሚታወስ ሲሆን የውድድሩ ቀላል ድልድል በተባለው ምድብ 4 ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ፤ ጋቦን፤ ብሩንዲና ሞውሪታንያ ተገናኝተዋል፡፡

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ የሚገኝ ስኬት የዓለም ዋንጫን ኃይል ሚዛን እንደሚወስን ታወቀ፡፡ የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ፤ የስፔኑ ላሊጋ፤ የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋና የጣሊያኑ ሴሪ ኤ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ላለፉት 10 ዓመታት የነበራቸው የበላይነት የየብሔራዊ ቡድኖቻቸውን ጥንካሬ በዓለም አቀፍ ውድድሮች አሳይቷል፡፡ በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ በሚሳተፉ 32 ብሄራዊ ቡድኖች የአውሮፓ ታላላቅ ሊጐች ልምድ በውድድሩ የሚገኝ ውጤትን ማንፀባረቁ የማይቀር ይሆናል፡፡
የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ምእራፍ ድልድል ሰሞኑን ሲወጣ ማንችስተር ዩናይትድ ከግሪኩ ክለብ ኦሎምፒያኮስ፤ ፓሪስ ሴንትዠርመን ከጀርመኑ ክለብ ባየር ሌቨርኩዘን፤ ሪያል ማድሪድ ከጀርመኑ ክለብ ሻልከ፤ ቦርስያ ዶርትመንድ ከራሽያው ዜኒት ፒተርስበርግ፤  ቼልሲ ከቱርኩ ክለብ ጋላታሰራይ፤ አርሰናል ከአምናው የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ባየር ሙኒክ፤ ማንችስተር ሲቲ ከባርሴሎና እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ ከኤሲ ሚላን  ተገናኝተዋል፡፡ የጥሎ ማለፉ ምእራፍ በፌብርዋሪ ወር የመጨረሻ ቀናት የመጀመርያ ጨዋታዎች ሲደረጉ የመልስ ግጥሚያዎች በማርች ወር መግቢያ ላይ ይደረጋሉ፡፡ከጥሎ ማለፉ ተፋላሚዎች ከፍተኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ልምድ ያለው ባርሴሎና ሲሆን በ1102 ጨዋታዎች በማድረግ ነው፡፡ ማን ዩናይትድ 952 ፤ቼልሲ 899 ፤ሪያል ማድሪድ 825 ፤ባየር ሙኒክ 768፤አርሰናል 594፤ ኤሲ ሚላን 558፤ ማንችስተር ሲቲ 500 እንዲሁም ፓሪስ ሴንትዠርመን 491 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች  ልምድ አላቸው፡፡ ዘንድሮ በዝውውር ገበያ ከፍተኛ ወጭ በማውጣት አንደኛ የሆነው በ163.5 ሚሊዮን ዩሮ  ሪያል ማድሪድ ሲሆን፤ ማን ሲቲ 116 ሚሊዮን ዩሮ፤ ፓሪስ ሴንትዠርመን 111 ሚሊዮን ዩሮ፤ ቼልሲ 75.4 ሚሊዮን ዩሮ፤ እንዲሁም ባርሴሎና 70 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ አድርገዋል፡፡ 16ቱ  ክለቦች  በአጠቃላይ የቡድን ስብስባቸው በትራንስፈር ማርኬት የዋጋ ተመን ሲወጣላቸው አንደኛ ደረጃ ያለው 583.5 ሚሊዮን ዩሮ የተተመነው ሪያል ማድሪድ  ነው፡፡ ባርሴሎና በ582.3 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ባየር ሙኒክ በ487.2 ሚሊዮን ዩሮ፤ ማን ሲቲ በ472.75 ሚሊዮን ዩሮ፤ ቼልሲ በ458.75 ሚሊዮን ዩሮ፤ ማን ዩናይትድ በ404 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ፓሪስ ሴንትዠርመን በ361.3 ሚሊዮን ዩሮ ፤አርሰናል በ355.5 ሚሊዮን ዩሮ፤ ቦርስያ ዶርትመንድ በ293.8 ሚሊዮን ዩሮ ፤አትሌቲኮ ማድሪድ በ255 ሚሊዮን ዩሮ፤ ኤሲ ሚላን በ219.5 ሚሊዮን ዩሮ ፤ዜኒት ፒተርስበርግ በ205 ሚሊዮን ዩሮ ኤፍሲ ሻልካ 04 በ184.3 ሚሊዮን ዩሮ ፤ጋላታሰራይ በ157.4 ሚሊዮን ዩሮ ፤ባየር ሌቨርኩዘን በ137.1 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም ኦሎምፒያኮስ በ72.3 ሚሊዮን ዩሮ በሚያወጡ የተጨዋቾች ስብስብ ተገንብተዋል፡፡
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በስሩ የ54 አገራት ፌደሬሽኖችን ቢያቅፍም ባለፉት 8 የሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ዘመናት ለግማሽ ፍፃሜ የሚደርሱ ክለቦች ከአራት የዓለማችን ታላላቅ ሊጐች ከሚካሄድባቸው ከስፔን፤ ከእንግሊዝ፤ ከጣሊያንና ከጀርመን ብቻ የሚገኙ ሆኗል፡፡ በዘንድሮው የሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ምእራፍ ከሚገኙ 16 ክለቦች አራት ከእንግሊዝ፤ አራት ከጀርመን እንዲሁም ሁለት ከስፔን ሊጎች ተወክለዋል፡፡ ከእነኚህ አገራት ውጭ ሌላ ክለብ ከሌላ አገር ለመጨረሻ ጊዜ የነበረው ከ9 አመት በፊት የሆላንዱ ፒኤስቪ አየንድ ሆቨን ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰበት ሲሆን ከፍተኛውን ውጤት ደግሞ በ1995 እኤአ ላይ አያክስ አምስተርዳም እና በ2004 እኤአ ላይ የፖርቱጋሉ ኤፍሲ ፖርቶ ዋንጫውን በማንሳት ያስመዘገቧቸው ታሪኮች ናቸው፡፡ድሮ የየአገሩ ትልልቅ ክለቦች ውጤታማ ይሆኑበት የነበረው የሻምፒዮንስ ሊግ መድረክ አሁን ለተወሰኑ አገራት ስኬታማነት የተመቹ መሆኑ የእግር ኳስን የኃይል ሚዛን አዛብቶታል፡፡
የአራቱ አገራት ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊግ ውጤታማነት መቀጠል የሊግ ውድድራቸውን አጠናክሮታል፡፡ የሊጎቻቸው መጠናከር ደግሞ በየብሄራዊ ቡድኖቻቸው ስኬት ላይ እየተስተዋለ ነው፡፡ የክለቦች ስኬት በእነዚህ አገራት መሰረቱን ሊይዝ የበቃው ባላቸው የአካዳሚዎች እና በወጣቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና ነው፡፡ በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከእንግሊዝ በስተቀር የጀርመን፤ የጣሊያንና የስፔን ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች ያላቸው ስኬት ለብሄራዊ ቡድኖቻቸው ጥንካሬ መገለጫ ሆኗል፡፡ ከ2006 እኤአ ወዲህ የስፔን ብሄራዊ ቡድን ሁለት ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ እንዲሁም አንድ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ድሎችን ሲያስመዘግብ ባለፉት ሁለት ኮንፌደሬሽን ካፕ ውድድሮች በሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ የብርና የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
የጣሊያን ብሄራዊ ቡድን በ2006 እኤአ የዓለም ዋንጫን ሲያሸንፍ በ2012 እኤአ ላይ በአውሮፓ ዋንጫ ሁለተኛ ደረጃን እንዲሁም በ2013 በኮንፌደሬሽን ካፕ የሶስተኛ ደረጃን ማግኘት ችሏል፡፡ በ2006 እና በ2010 እኤአ ላይ በተደረጉት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች ሶስተኛ ደረጃ ያገኘው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በ2008 እኤአ በአውሮፓ ዋንጫ በሁለተኛ ደረጃ ጨርሷል፡፡
ከ1996 እኤአ ወዲህ በዓለመ አቀፍ ውድድር ዋንጫ አግኝቶ የማያውቀው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በብራዚል 20ኛው ዓለም ዋንጫ ዋንጫውን በማንሳት የመጀመርያው በደቡብ አሜሪካ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃ አውሮፓዊ ቡድን ለመሆን በከፍተኛ መተማመን ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡በ20ኛው ዓለም ዋንጫ በደቡብ አሜሪካ እና በአውሮፓ ቡድኖች መካከል የሚኖረው ፉክክር ትኩረት መሳቡ የማይቀር ቢሆንም ጀርመን፣ ስፔንና ጣሊያን በሊጐቻቸው ጥንካሬ እና በክለቦቻቸው ውጤታማነት ከፍተኛ ግምት ይወስዳሉ፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በእንግሊዝ፤ ስፔን፤ ጀርመንና ጣሊያን የሚካሄዱት አራቱ ታላላቅ ሊጎች በሻምፒዮንስ ሊግ ውጤታማነት የያዙት ብልጫ በቅርብ ጊዜ የሚቀናቀነው አይኖርም መባሉ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርን አስጨንቆታል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ በክለቦች የፋይናንስ አቅም የተፈጠረው የብቃት ልዩነት እና የቡድን ስብስብ መጠናከር የዓለም ዋንጫን የበላይነት መወሰኑን ለመገደብ ክለቦች በፋይናንስ እንቅስቃሴያቸው ስፖርታዊ ጨዋታነት እንዲኖራቸው ያወጣውን ገደብ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር መፍትሔ እንደሚሆን ይገልፃል፡፡ በቲቪ መብት፤ በስፖንሰርሺፕ እና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የባለሃብት ትኩረትን በመሳብ ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ በሻምፒዮንስ ሊግ ያለውን የበላይነት ፈጥሮታል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት ሩስያዊው ሮማን አብራሞቪች ቼልሲን በባለቤትነት ከያዙ ጀምሮ ዘንድሮ ኤንዶኖዢያዊ የሚዲያ ኢንቨስተር ኢንተርሚላንን በባለቤትነት እስኪገዛ በርካታ ባለሃብቶች ለአራቱ ምርጥ ሊጎች ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ ከሆኑ 20 ክለቦች 11 በውጭ ባለሃብቶች ተይዘዋል፡፡ በስፔን እና ጣሊያን  ክለቦች እዳ በማብዛታቸው እና በጀርመን  ክለቦች የባለሃብት ድርሻ በ49 በመቶ ድርሻ መወሰኑ ወደ እንግሊዝ እንዲያመዝን ምክንያት ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን የኤሽያ ከበርቴዎች፤ የዓረብ ሼኮች፤ የሩስያ ነዳጅ ቆፋሪዎች እንዲሁም የአሜሪካ ነጋዴዎች በተለይ ለአራቱ ሊጎች የሰጡት ትኩረት ክለቦቹን አጠናክሯቸዋል፡፡ በቅርብ ተፎካካሪነት እየተከተለ የሚገኘው የፈረንሳዩ ሊግ 1 ነው፡፡ ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት ከፈረንሳይ ክለቦች መካከል ፓሪስ ሴንትዠርመንና ሞናኮ በሃብታም ሰዎች ባለቤትነት መገዛታቸው ይታወቃል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች 504 ተጨዋቾች  በዝውውር ገበያ አጠቃላይ ዋጋቸው እስከ 3.8 ቢሊዮን ዩሮ ይገመታል፡፡ በስፔን ላሊጋ ክለቦች 481 ተጨዋቾች  2.6 ቢሊዮን ዩሮ፤ በጣሊያን ሴሪኤ 574 ተጨዋቾች 2.4 ቢሊዮን ዩሮ እንዲሁም በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ክለቦች 511 ተጨዋቾች  2.05 ቢሊዮን ዩሮ  ይተመናሉ፡፡

Monday, 23 December 2013 09:47

ነበር እና ነውር!

“በነውሯ የምትኮራ ፍየል ናት!”

“ነበር” የሚለው ቃል ቀለል ባለ መንገድ ሲታይ የአንድን ግለሰብ ያለፈ ታሪክ፣ ወይም የአንድን ድርጊት ትዝታ ለማስታወስ የምንጠቀምበት ቁጥብ መግለጫ ነው፡፡ “ነውር” የሚባለው ደግሞ አንድ ማህበረሰብ የሚነቅፈው፤ የሚጠየፈው፤ በመንቀፉና በመጠየፉም እንዳይደረግ የሚያወግዘው ድርጊት ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ የውሻ ሥጋ መብላት በህግ አልተከለከለም፤ ግን ማህበረሰቡ “ነውር” ስላደረገው አይበላም፡፡ ይህንን ድርጊት የሚፈፅም ሰው ቢገኝ “ነውረኛ” ነው፡፡ ማህበረሰቡ ባልተጻፈ ህግ ከልክሎታላ! በአንዳንድ ማህበረሰቦች ዘንድ በአደባባይ ከንፈር ለከንፈር መሳሳም “ነውር” ነበር። የመሳሳሙ ነውርነት ግን በአደባባይ ሲሆን ነው እንጂ በጨለማና በድብቅ ቦታዎች ይፈቀዳል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ “ነበር”ን እና “ነውር”ን እያፈራረቁ ማስቃኘት ሲሆን “ነውር” ይባል የነበረው ወደ “ነበር”ነት እየተቀየረ መሄዱን፤ አንዳንዱ እንዲያውም ሌላ መልክ መያዝ መጀመሩን ማሳየት ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቅዱስ ቁርዓን ጉቦ ነውር ነው፤ ነውር ብቻ ሳይሆን በሰማዩ ችሎት ከፍተኛ ቅጣትን ሊያስከትል የሚችል ወንጀል ተደርጐ ይወሰድ ነበር፡፡ አሁን ግን “ነውር” አይደለም፤ እንዲያውም የስልጡንነትና የ”አራዳነት” መለያ እየሆነ መጥቷል፡፡ ህብረተሰቡ በጉቦ የተገዛውን ዘመናዊ መኪና ወይም ቤት ሲያይ “ይህ ነውረኛ! ይህን መኪና ወይም ቤት የገዛውኮ በነውረኛነት ባገኘው ገንዘብ ነው” አይልም፡፡
እንዲያውም በተቃራኒው ነውረኛነቱን ረስቶ ልክ ሠርቶ እንዳገኘው ሁሉ ስለጀግንነቱ በአድናቆት ማውራትን ይመርጣል፡፡ ስለዚህ “ነውሩ” ነበር ሆነ ማለት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ባሉ የስልጣን እርከኖች ዓይንአውጣ ጉቦኞች እንደ አሸን እንዲፈሉ እገዛ እያደረገላቸው ነው፡፡
በህግም ሆነ በሃይማኖት መጻሕፍት የተወገዘ ከመሆኑም በላይ ያልሠሩበትን መብላት፣ ወይም የሌላ ሰው ንብረት መስረቅ “ነውር” ነበር፡፡ አሁን ግን “ሥራ” ሆኗል፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት “መስረቅ ሥራ ነው፤ ወንጀል የሚሆነው ሌባው ሲያዝ ብቻ ነው” ማለታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ለዚህም ነው “ነውር ነበር ሆኗል” የምለው፡፡
በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አንድ ሌባ ነበረ አሉ፤ በተደጋጋሚ እየሰረቁ ህዝቡን ሲያስቸግሩ የወቅቱ የፍትህ ሚኒስትር የነበሩት አፈንጉሥ ነሲቡ መስቀሎ፤ አንድ ሥርዓት ማበጀት ግድ ሆነባቸው። እሱም ጥፋታቸው በማስረጃ ሲረጋገጥ አደገኛ ሌቦችን ግንባራቸውን በጋለ ብረት መተኮስ ነው፡፡ ግንባሩ ላይ ጠባሳ ያለበት ሁሉ “ነውረኛ ሌባ” ስለሆነ ህዝቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ያደርግ ጀመር፡፡ ሌቦችም የዋዛ አልነበሩምና ሻሽ ግጥም አድርገው በማሰርና ጨዋ በመምሰል እንደ ለመዱት ወደ ዝርፊያቸው ገቡ፡፡
አፈ ንጉሥ ነሲቡም ከሌቦች የላቀ ችሎታ ነበራቸውና የሌቦችን ማታለያ ወዲያው ደረሱበት፡፡ ስለዚህ ሌባ ተይዞ ሲመጣላቸው መጀመሪያ ሻሹን ያስወልቁና ጠባሳ ያለበትና የሌለበት መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ ግንባሩ ላይ ጠባሳ ካገኙበት የለመደ ወንጀለኛ ነውና በጋለ ብረት የመተኮሱን ቅጣት አፍንጫው ድረስ ዝቅ አስደረጉት፡፡ ምክንያቱም አፍንጫውን በሻሽ ሸፍኖ መሄድ ስለማይችል ሌብነቱን በቀላሉ ያጋልጥበታል ማለት ነው፡፡ አሁን ያ አይነቱ ቅጣት ነውር ቢሆንም ስርቆቱ ግን መልኩን እየቀያየረ ቀጥሏል፡፡
በዕድሜ ታላቅ የሆኑ ሰዎች ሲመጡ ከተቀመጡበት መነሳትና ቦታውን ለእነሱ በመልቀቅ ማክበር የተለመደ ነበር፡፡ አሁን ግን በተቃራኒው እየሆነ ነው፤ እርግጥ ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም አንዳንድ ወጣቶች አሁንም ታላቆቻቸውን ያከብራሉ፣ በማክበራቸውም አንጀት የሚያርስ ምረቃ ያገኛሉ፡፡
ጥፋቱ የወጣቶች ብቻ አለመሆኑንም ልብ ማለት ይገባል፤ አንድ ቀን በስድስት ቁጥር አውቶብስ ተሳፍሬ ወደ አዲሱ ገበያ በመጓዝ ላይ ሳለሁ፣ አንዲት ዕድሜያቸው በስልሳዎቹ የሚገመት ወይዘሮ መጡና አጠገቤ ቆሙ፤ ከመነሻ አካባቢ ስለተሳፈርሁ ወንበር ላይ ነበር የተቀመጥሁት፡፡ ባህሌን ለማክበር፤ ታላቄ ቆመው የእኔ ወንበር ላይ መቀመጥም “ነውር” መሆኑን ስለማውቅ ከተቀመጥሁበት ተነስቼ “እዚህ ጋ ቁጭ ይበሉ” አልኋቸው፡፡
ሴትየዋ ግን ለፈፀምሁት ትሁት ድርጊት ከማመስገን ይልቅ “አንት ሌባ  አወቅሃልሁኮ የታባህና፤ ደሞ እንደማላውቅህ ቁጭ በይ ትለኛለህ? ነቅቸብሃለሁ አንት መልቲ…  ያላወረዱብኝ የስድብ አይነት አልነበረም፡፡ ሰው ሁሉ ወደኔ ሲዞርና ነገሩን ማጋጋል ሲጀምር በውስጤ የነበረው ትህትና ሁሉ እንጥፍጣፊ እንኳ ሳይቀር ሙልጭ ብሎ ጠፋ፡፡
እናም ሳላስበው ከታላቋ ሴትዮ ጋር እንካ ስላንትያ ገጠምሁ፡፡ የምወርድበት ቦታ ቅርብ ባይሆን ኖሮ ምንአልባትም ወደ ዱላ ሳናመራ አንቀርም ነበር፡፡ የዚያን ዕለቱ ትህትናዬም በነበር ቀረ፡፡ ከዚያ በኋላም ሰውን ለማክበርም ላለማክበርም አቅማማ ጀመር፡፡
በአደግሁበት አካባቢ አንድ ሰው በአጠገባችን ሲያልፍ አወቅነውም አላወቅነውም “እንደምን አደርህ?” ማለት የተለመደ ነበር፡፡ ይህንን ሳያደርግ በነዋሪዎች ፊት ሲያልፍ በነበረ ግለሰብ ላይ በአንድ ወቅት የዱላ ቅጣት ሲፈፀምበት በዓይኔ በብረቱ አይቻለሁ፡፡ በደርግ ጊዜ ግን “ኮሙኒስቶች” እየበዙ በመሄዳቸው “እንደምን አደርህ” በማለት ፋንታ “ታዲያስ” ማለት ተጀመረ፡፡
“እንደምን ነህ ብለው እንደምን ነህ አለኝ፤
እግዚአብሔር ይመስገን ሊቀር ነው መሰለኝ”
የተባለው ህዝባዊ ግጥም የተነገረውም በዚያ ዘመን ነው፡፡
ምክንያቱም “እንደምን አደርህ?” ሲባል ክርስቲያን ከሆነ “እግዚአብሔር ይመስገን!” ሙስሊም ከሆነም “አላህምድሊላህ!” ይላል እንጂ መልሶ “እንዴት ነህ?” ወይም “ታዲያስ” የሚል መልስ መስጠት ከነባሩ ሰላምታ ማፈንገጥ ስለሆነ ነውር ነው፡፡ አሁን ግን “ነበር” እየሆነ ይመስለኛል። ዛሬ ዛሬማ እንዲያውም በ”እንደምን አደራችሁ?” ፋንታ “ፒስ ነው?” የሚል ፍርንዱስ (ጉራማይሌ) ሰላምታ ተጀምሯል፡፡
“ዘመናዊ” በሚባለው ህብረተሰብ ውስጥ በየአጥሩ ስር መፀዳዳት ነውር ነው፤ ይህ ዓይነቱ ነውረኛ ድርጊት የመረራቸው የጐንደር ከተማ ነዋሪዎች “ጨዋ ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ “መፀዳዳትን ከድመት ተማሩ!” የሚል ማስታወቂያ ለጥፈው ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡
እርግጥ ያነጋገርኳቸው አንዳንድ ሰዎች “ከድመት በታች አድርገው ስላሰቡን ከድመት ተማሩ አሉን” በማለት ቅሬታቸውን ገልፀውልኛል። ግንኮ ማስታወቂያው ይገርማል፡፡ ድመቶቹን ልብ ብለን አይተናቸው ከሆነ ከተፀዳዱ በኋላ አፈር ያለብሱታል፡፡ በዚህ ረገድ ከሰው የተሻለ ተፈጥሮ አላቸው ማለት ነው፡፡ ሰው ግን በተለይ የከተማ ነዋሪ የራሱን ጤና በራሱ የሚዋጋ የዋህ አይነት ሆኖ ይሰማኛል፡፡
ይህን በተመለከተ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በአንድ ወቅት “የኢትዮጵያ ህዝብ ሲበላ ተደብቆ ነው፤ ግን በኩራት ተጀንኖ በየአደባባዩ ይፀዳዳል” ሲሉ በተለመደ ብስጭታቸው መናገራቸውን የዕድሜ እኩዮቼ ታስታውሳላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡
ለነገሩ ነውሩን ያባባሱት የከተማችን ማዘጋጃ ቤትና ባለ ሆቴሎች ናቸው፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ በቂ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች የሉትም፤ የዚህ ዓይነቶቹ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በብዛትና በጥራት ሳይገነቡ “አጥር ስር መፀዳዳት ያስቀጣል፤ መሽናት አምስት ብር ያስቀጣል…” የሚል ማስታወቂያ መለጠፍ ብቻውን ነውሩን ሊያስቀርና ጤንነታችን ሊጠብቅልን አይችልም፡፡ የኩላሊትና የሽንት ቧንቧ በሽተኛው፣ ሰካራሙ፣ ሥርዓት አልባው፣ ወዘተርፈው ሁሉ “አጥር ሥር የሚፀዳዳ ውሻ ብቻ ነው!” የሚል ጽሑፍ እያነበበ “ዛሬ ውሻ ነኝ” ብሎና ሰራሱ የውሻነት “ክብር” እያጐናፀፈ የህብረተሰቡን ጤና በእጅጉ የሚጐዳው ከንቱ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
ሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶችና ሌሎች መሰል ተቋማትም ምግብና መጠጥ እየሸጡ፣ መፀዳጃ ቤቶችን በቁልፍ ይከረችማሉ፤ ክፍሉ ለምን እንዳስፈለገም የገባችው አይመስሉም፡፡ እነሱ ቤት ውስጥ በልቶና ጠጥቶ የት ሄዶ ሊጠቀም እንደፈለጉም አይታወቅም ወይም ሥልጣኔ ይጐድላቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ጨዋው ሰው ሳይቀር ሜዳ ላይ መፀዳዳት ግድ ይሆንበታል፡፡
በአጠቃላይ “ነውር”ን እና “ነበር”ን ስናነፃፃራቸው፣ ነውራችን ሜዳ ላይ እንደ ገብስ እየተሰጣ ጥንካሬያችን፣ ወጋችንና ክብራችን “ነበር” እየሆነ መጥቷል፡፡ መፈቃቀር፣ መከባበርና መተባበር ፌዝ እየሆነ በነባሩ ማንነታችን ላይ ጥቁር ጥላውን እያጠላበት ይመስለኛል፡፡
በቅኝ ግዛት ማንነታቸውን የተነጠቁ ህዝቦች የጠፋ ማንነታቸውን ፍለጋ ሌት ከቀን በሚዋትቱበት በአሁኑ ወቅት በነውራችን እየፈከርን፣ በታሪካችን እያፈርንና በአጉል ዝባዝንኬ ጉዳዮች እየተዋጥን ስንሄድ ቆም ብሎ ማመዛዘን ካቃተን፣ የልጆቻችን ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመቱ አይከብድም።
ስለሆነም ነውራችንን እንወቅ፤ አውቀንም እናስወግድ፡፡ ነባር ባህሎቻችንና ልምዶቻችን ጐጂ እስካልሆኑ ድረስ በወጉና በክብር እየጠበቅን እንጠቀምባቸው፤ “በነውሯ የምትኮራ ፍየል ናት” ይባላልና!   

Published in ህብረተሰብ

ትውልድ በሠልፍ እንደሚያልፍ ሠራዊት ነው። ልዩነቱ ሠልፈኛው በየራሱ ተራ ጥሎት የሚሄደው ነገር ለሚቀጥለው ትውልድ የሚኖረው ፋይዳ ወይም የሚያቆየው ጥፋት ነው፡፡ ትናንት ስለ ዛሬው ትውልድ በየመስኩ መሥዋዕትነት የከፈሉ እንዳሉ ሁሉ መራራ ሥር ያቆዩ፣ ትውልዳቸውንና ቀጣዩን ትውልድ በጥቅም የሸጡ ወይም ከዚያ አልፈው በቸልተኝነት አድርባይ ሆነው የኖሩ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በፖለቲካው፣ በኪነጥበቡና በኢኮኖሚው ዘርፍ ያቆየው እኩይና ሠናይ ነገር መገለጫ ነው፡፡
ከላይ ያልኳቸው ነገሮች በየሀገሩና በየፖለቲካ ምህዳሩ ኖረው ዛሬም ድረስ በየትውልዱ ጭንቅላት ላይ በበጐ ወይም በክፉ ይሽከረከራሉ፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካው ዴሞክራሲ መልክ እንዲኖረው አንገታቸውን ገመድ ውስጥ የከተቱ ጐበዞች ነበሩ፤ ለሕዝብ ነፃነት ሣይተኙ አድረው ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ ይህን ያህል ካስተዳደርን ይበቃናል፣ እኛ ዛሬ ከተሳሳትን ቀጣዩ ትውልድ ነገ ይሣሣትበታል ብለው ያበቁ ነበሩ፡፡ ጀፈርስን ሁለት ዙር በፕሬዚዳንትነት ከቆየ በኋላ ሦስተኛ ዙር እንዲወዳደር ሲጠይቁት፤ “ዛሬ በእኔ ካዩት ነገ ይደግሙታል” ነው ያለው። ከዚህ የባሰም አለ፡፡ የሕንዱ ማህተመ-ጋንዲ ለዓመታት የተሰደደለት፣ የታሠረለትና የተንገላታለት የሀገር ነፃነት ጥያቄ መልስ አግኝቶ “እነሆ ሥልጣን!” ሲባል “አሻፈረኝ” ብሎ የፍዳውን ገፈት ለራሱ፣ ነፃነቱንና ሥልጣኑን ግን ለሕዝብ ሰጥቶ ነበር፡፡ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኔልሰን ማንዴላም ለሃያ ሰባት ዓመታት እሥር ቤት የማቀቁለትን ነፃነት፣ ለሕዝባቸው ካስጨበጡ በኋላ ዙፋን ሞቋቸው፣ ድሎት አጓጉቷቸው “በቀላሉማ አልለቅም!” አላሉም፡፡ ሥልጣኑን ለሕዝብ አስረክበዋል፡፡ ይህ ማንነታቸው ደግሞ ለደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ብቻ ሣይሆን ለመላው ዓለም ብዙ ነገር አስተምሯል፡፡ ወደ እኛ ስንመጣ ብዙ ነገሮቻችን ተበላሽተዋል፡፡ እንኳን በፖለቲካ ሥልጣን ሽግግር፣ ከሞያ ማህበራት እንኳ ሥልጣን መልቀቅ የሚከብዳቸው እንዳሉ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ በሃይማኖት ተቋማትስ ቢሆን? ስንት ሽኩቻ፤ ስንት ዱላ መማዘዝ አለ አይደል? ይህ ሁሉ ግን የውድቀት መጀመሪያ ነው፡፡
አሁን አሁን የምናወራቸው ወሬዎች አዲሱ ትውልድ ላይ ያፈጠጡ ቢሆኑም በቀጥታ የሚመለከቱት ግን ሁላችንንም ነው፡፡ “የማይረባ ትውልድ!” በማለት ዛሬ ለምንወቅሰው ትውልድ ያወረስነው ነገር ቢኖር የጦርነትና ደም መፋሠሥ ታሪክ ነው፡፡ የምንፅፍለት፣ ስለ ጦርነት፣ ቀለል ቢል ስለ ወሲብ ነው፡፡ ያ ብቻም አይደለም። ዘመኑ ከቀደመው ዘመን የተለየና በቴክኖሎጂ የቀበጠ ነው። የዓለም አቀፍ ቅብጠቶችና ዕብደቶች በኢንተርኔት በየጓዳው ይገባሉ፡፡ ፈረንጅ የመምሠል አባዜም ተከትሎ ይመጣል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በጐ ነገር የሚያስተምሩ፣ ራሣቸውን ስለ ሕዝባቸው የሰጡ አርአያዎች የሏትም ማለት አይደለም፡፡ ብዙ ጀግኖች ስለ ነፃነትና የሀገር አንድነት ሞተዋል፡፡ ብዙዎች የጣፈጠ እንጀራቸውን ትተው ከሕዝቡ ጋር ተቆራምደው ዘመናቸውን ጨርሰዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፉት አርባ ዓመታት እንኳ የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር ሲሉ በግንባር ያለፉት ጀግኖች ቁጥር በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ይሁንና አሁን ግን ወድቀናል ማለት ይቻላል፡፡ የወደቅነው እነማን ነን? ካልን የቀደመው ትውልድ ቅሪቶችን ጨምሮ ሁላችንም ነን፡፡ ለውድቀታችን ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ፣ የጠነከረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት መውደቅ ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ የጐሳ ፖለቲካው በውስጣችን የፈጠረው የመለያየት አባዜ አስተዋፅኦው የላቀ ነው፡፡ እናም ከሠፈር ያለፈ ሕልም በማጣታችን ምክንያት አርቆ ማሠብ የተሣነን ይመሥላል፡፡ አንድ ሰው ከራሱ ክልል ውጭ ማሰብ ካቃተውና ማንነቱን ካጠበበ፣ የቀደሙ ጀግኖችና አዋቂዎችንም በዘር ስለሚሸነሽን፣ ከራሱ ክልል ውጭ የሚያየው አርአያም አይኖረውም፡፡ ከዚህም ባለፈ አንድ ሰው አቅም ኖሮት እንኳ የተወለደበት ብቻ ሣይሆን የክልሉ ተወላጅ ካልሆነ ዕውቀቱን ለሀገሩ የሚያውልበት ዕድል እንኳ እያጣ ነው፡፡ ይህ ዋናው የፖለቲካ ሥርዓቱ ቀውስ ይሁን እንጂ ኪነ-ጥበቡና ሃይማኖቱም ለውድቀታችን ተጠያቂ ናቸው፡፡ በእኛ ዘመን እንደ አቡነ ጴጥሮስ ለነፃነትና ለእውነት ሕይወቱን የሚሰጥ፣ ደረቱን ለጥይት የሚያሰጣ መሪ አለ ወይ? ብሎ መጠየቅ በራስ መሣለቅ ነውና ዝም ብሎ ማለፍ የሚሻል ይመሥለኛል፡፡
በኪነጥበቡ ዘርፍ ከመጣን ደግሞ ኪነጥበቡ ልክ በሀገሪቱ እንዳሉት ብዙ ነገሮች ባለቤት ያጣ ይመሥላል፡፡ ባለቤቶቹ ሊሆኑ የሚገባቸውም በዐይን የሚገቡ ሰዎች፣ በአብዛኛው በጥቅም ራሳቸውን ሸጠዋል፡፡ ስለ ሕዝብ ነፃነት፣ ስለ ጥበብ ዕድገት አያገባቸውም፡፡ የነርሱ ሻሞ ለጭብጨባና ለጥቅማጥቅም ብቻ ነው፡፡ እነርሱ ከ”ሸቀሉ” ሕዝብ ገደል ይግባ! እንኳን ለሕዝብ ለማማጥና ለመታመም ቀርቶ ሕዝብ አልቆ ባዶ መድረክ ላይ ቢነግሱ የሚወድዱ ይመሥላሉ፡፡ ለዚህ እማኝ የሚሆነን የዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ሶማሌ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አከባበርን በተመለከተ የነበሩት ሽኩቻዎች ናቸው፡፡ እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ቅንና ደግ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ብዙዎቻችን እናውቀዋለን፡፡ ሕዝቡን አሁን ካለው ፖለቲካዊ ትርምስ ውጭ ስናየው፣ ውብና ቀለል ያለ ኑሮ የሚመርጥ፣ ጭንቅ የማይወድ፣ ልበ-ሙሉም ነው፡፡ ግን ብዙዎች ይህንን ውበቱን አይደለም፣ ያደነቁት፣ ይልቅስ ኪሱን ነው የነቀነቁት። እርስ በርሱ እንደሚናቆር ጥንብ አንሳ፣ የነበረውን መናቆር ያየና የሰማ ያውቀዋል፡፡
ያለ ምንም ማጋነን ለድንበራቸው እንደሚሞቱት፣ ሕዝባቸውን እንደሚያስቀድሙት አባቶቻችን አይደለንም-ወድቀናል፡፡ በጥበቡ መስክ ተሠልፈናል የምንለው ሰዎች፤ ጥበብ አራት እግርዋን ብትበላ ግድ እንደሌለን የሚያሣዩ ብዙ ጠባሳዎች አሉን፡፡ ስመ-ጥር የተባሉ ሰዎች መጽሐፍትን ሣያነብቡ እንኳ የጀርባ አስተያየት እስከመስጠት ይዘቅጣሉ፤ ሌሎች ለገበያ ሲሉ በአደባባይ ላይ የውሸት ምስክርነት ሲሰጡ ሕሊናቸው አይገስፃቸውም፡፡
የጥበቡን ድንኳን ባይረግጡ እንኳ ደጁ ላይ ነን የሚሉት በየትኛውም ሁኔታ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ከማድረግ ያለፈ ሕልም ያላቸው አይመሥሉም፡፡ ለምሳሌ እንኳ ብጠቅስ “ጥርሴ” በሚል ርዕስ አንድ የግጥም መጽሐፍ ያሣተመች ወጣት፤ ከቅንነት ይሁን ከታላቅነት ማማ ላይ በመውጣት ጉጉት ተመሥጣ፣ በመጽሐፍዋ ጀርባ ላይ አስተያየት ያፃፈችው የስፖንጅ ፋብሪካውን ባለቤት አቶ አቤሴሎም ይህደጐንና ሻለቃ ሃይሌ ገብረሥላሴን መሆኑ ገርሞኛል፡፡ ለመሆኑ ጥበብ የራሱ ቤተሰብ የለውም? የጀርባ አስተያየት ለማፃፍስ ጥበቡን ያለ ቦታው መጣል ያስፈልጋል? አንድ ሥነ-ጽሑፍ የሚገመገመው ገንዘብ ወይም ዝና ባለው ሰው ሳይሆን በዘርፉ ላይ ባለው ዕውቀትና አተያይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ይሁንና ያንን የመሳሰሉ ስህተቶች እየተፈፀሙ ነው፡፡ ይህም የዘመናችን ውድቀት አንድ አካል ነው፡፡
ትውልድን መቅረፅ አለበት የምንለው የጥበብ መሥመር፤ ይባስ ብሎ ቁልቁል ወደ ገደል ለመገፍተር በገንዘብ እየተሸቀጠ ነው፡፡ ገበያ አላቸው የሚባሉት ልቅ የወሲብና የፖርኖግራፊ ጽሑፎች ገበያውን እየወረሩት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ “ጭን” በሚለው ርዕስ ሥር እየተፃፉ ትውልዱን ከምርምርና ከዕውቀት ይልቅ የወሲብ ባሪያ ለማድረግ እየተጣደፉ እንደሆነ መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው፡፡
ወደ ሙዚቃ ሥራዎቻችንም ሥንሄድ፣ አባቶቻችን ባወረሱን መስመር ላይ አይደለንም። የዘፈን ግጥሞቻችን ትውልድን በበጐ ሥነ-ምግባር ከመቅረፅ ይልቅ፣ አባቶች ያቆዩትን የሥነ ምግባር አጥር እያፈረስን ስድ በመልቀቅ ላይ ነን፡፡ ከዚህ ቀደም የምንሰማቸውን ዓይነት ጥልቅ ሀሣብ፤ የሰው ልጅ ሕይወት ጠቃሽ ፍልስፍናዎችን መሥማት የሕልም እንጀራ ሆኗል፤ ያም ሳይበቃ “ሳይደክሙ ዳር መድረስ” በሚል ፍልስፍና፣ ሌሎች የደከሙበትን ግጥምና ዜማ ነጥቆ ለጆሮ በሚቀፍ ዜማ እንደጅብ መጮህ ተለምዷል።
የሚያሣዝነው የነጣቂው መብዛት ብቻ አይደለም። ሁሉም ነገር ባለቤት ማጣቱ ነው፡፡ በጐ ነገሮቻችን በሙሉ እየተዘረፉ በምትኩ አሣፋሪ ነገሮቻችን ጌጥ ሆነውን አደባባይ ላይ እየተንፏለሉ ነው። አንድ ፊልም ላይ ጥበቃ ሆኖ የሠራው ወይም አጃቢው “አርቲስት እገሌ እባላለሁ” እያሉ-ትከሻ ማሳበጡ ሁሉ የውድቀታችን ደወሎች ናቸው። ደወሉን የሚሠማ ጆሮ ግን የጠፋ ይመሥላል። ጋዜጠኞች ብንሆን፣ ወይ ለመንግስት እናሽቃብጣለን-ለሣንቲም! ወይ ደግሞ በጭፍን እንሣደባለን ለእንጀራ!
የእኛ ነገር ስላለፈው ዘመን ማውራት ብቻ ነው፡፡ የታገል ሰይፉ ግጥም እንዲህ ትለናለች፡-
“ዛሬም የዋርካ ልጅ”
ከዛፍ ግንድ ተቆርጠን …
ከከፍታ ወድቀን … ካፈር ተፍገምግመን
ከእንጨት ተፈልጠን …
ከጭራሮ ደርቀን-በቅጠል ተለቅመን፣
በማድቤት ነበልባል…
ተቃጥለን በፍም እጅ-አመድ ሆነን በነን
“ማናችሁ?” ስንባል…
ዛሬም “የዋርካ ልጅ” የምንል እኛ ነን፡፡
በርግጥም ዛሬም በአንድ እጃችን ምኒልክን ይዘን፣ በሌላው እጃችን ሌላ ይዘን ልንዘምር ይቃጣናል፡፡ የምኒልክ ወይም የአሉላ ልጅ ነን እያልን አሉላን ለመምሠል አንሞክርም! እንደ ጌጥ ስም ማንጠልጠል ሆኗል ስራችን፡፡ ብቻ ወድቀናል፤ ለመነሣት ወደ መሠላሉ ካልተጠጋን እዚያው እንዳንቀር እሰጋለሁ፡፡

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ከረማችሁሳ!
“ሄሎ!”
“ሄሎ ማን እንበል?”
“አታላይ በፍረዱ፡፡”
“አቶ አታላይ ከየት ነው የሚደውሉት?”
“ከወይራ ሰፈር፡፡”
“እሺ በተነሳው ጉዳይ ላይ ሀሳብዎን ይግለጹ፡፡”
ሀሳብ አለን…በሞሪንሆና ቬንገር መካከል ስላለው ‘እንካ ስላንትያ’ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉዳዮችም… “በተነሳው ጉዳይ ላይ ሀሳብዎን ይግለጹ…” የሚለን እንፈልጋለን፡፡ ሁሉም ተልጦ፣ ተከትፎ፣ ተዘልዝሎ ድስቱ ከተጣደ በኋላ…  “የዚህ ሰፈር ነዋሪ እንዲህ፣ እንዲህ አድርግ ተብለሀል!” አይነት ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
እናላችሁ…ብዙ ነገር… አለ አይደል… መከተፉንና መላጡን ሹክ የሚለን እየጠፋ ‘ድስቱ ከተጣደ’ በኋላ እያየነው ተቸግረናል፡፡
ለነገሩ ምን መሰላችሁ… ሀሳብ ለመስጠትም እኮ ችግር አለ፡፡ አሀ…ዘንድሮ ሀሳብን በጥሬው መውሰድ ቀርቷል፡ ልጄ…ከአፍ የወጣ ቃል እንደተፈለገው ቋንጣ ይሆንላችኋል! ኳስም አወራችሁ፣ ‘ባቡር’ም አወራችሁ… ‘ቦተሊካ ተች’ ይሰጠውና የቡድንና የቡድን አባቶች ሳትሉ አንደኛው ቡድን ውስጥ ትደለደላላችሁ፡፡
ልክ ነዋ… “የሳይንስ ትምህርት ለአገር ዕድገት ወሳኝነት እንዳለው አቶ አምታታው በዘዴ ለስብሰባው አስገነዘቡ…” የሚለው ወሬ ‘ሰበር ዜና’ በሚሆንባት አገር ነገርዬው “ወይ ከእኛ ጋር ነህ፣ ወይ ከእነሱ ጋር ነህ፣” ሆኗል፡፡
ስሙኝማ…ኤፍ.ኤም ላይ አድማጮች ሰጡ የተባለውን ‘ሀሳብ’ ስትሰሙ…ግራ ይገባችኋል፡፡ “አሁን ይሄ ጊዜውን ሰውቶ ጆሮውን ለፕሮግራሙ ለሰጠው ሰው ምን ይጠቅመዋል…” ያሰኛችኋል፡፡ ልክ ነዋ… አሰሱንም ገሰሱንም መድገሙ የአየር ሰዓት መሙያ ያስመስላላ!
እናላችሁ…ስለ ፊልም ጽሁፍ የሚያትቱ መጽሀፎች ምን ይሉ መሰላችሁ…ታሪክን ማጦዝ ያቃተው የፊልም ጽሁፍ ጸሀፊ በመኪና ማሳደድና በተኩስ ይሞላዋል ይላሉ፡፡ እኛ ደግሞ…የፕሮግራሙን ሦስት አምስተኛ  “በፕሮግራማችሁ ተመችቶኛል…” እና “ብርድ ስለሆነ ሞቅ ያለ ዘፈን ጋብዙን…” በሚል ሲሞላ በቃ…“ሰዎቹ የአየር ሰዓት መሙያ አጥተው መሆን አለበት…” እንላለን፡፡
  “እሺ፣ እኔ መናገር የምፈልገው አንዳንድ የመንግሥት ባለስልጣናት ባለጉዳይ…”
 “ይቅርታ አድማጫችን፣ አሁን የምንነጋገረው ስለ ባለስልጣናት ሳይሆን ስለመሥሪያ ቤቶች አሠራር ነው…”
የ‘ዋርካዎችን ስም’ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ጠርቶ ማን ይጠጣል! “እስኪጣራ ድረስ ማን ይጉላላል…” እንዳለችው እንሰሳ ልጄ… ‘እስኪጣራ ድረስ’ ብልጥ መሆን ነው፡፡ (“የሚጣራው ምንድነው?” የሚለው ጥያቄ እንደሚያሳስባችሁ ሁሉ እኔንም ያሳስበኛል፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… “አድማጫችን ማን እንበል?” ሲባል…ሰዎች ስማቸውን ሲናገሩ አንዳንዴ የ‘ቁጩ’ ስም እንደሆነ ከቃናቸው ትጠረጥራላችሁ፡፡ ምን ይደረግ…ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ዘንድሮ ስምም የግለሰብ መጠሪያነት ብቻ መሆኑ ቀርቶ በአንዱ ወይም በሌላ የ‘ቦተሊካ’ ቡድን የሚያስደለድልበት ዘመን ሆኗል፡፡
“ግን፣ እሱ ሰውዬ ስሙ ማነው?”
“እንትና እንተና ይባላል፡፡”
“ነው እንዴ! እኔም’ኮ አንዳንዴ ከአነጋገሩ እጠረጥር ነበር፡፡”
“ማለት…”
“ማለትማ የእንትና ደጋፊ ነው፡፡”
“በምን አወቅህ?”
“ይሄ ደግሞ፣ ከስሙ በላይ ምን ማረጋጋጫ ትፈልጋለህ!”
እናላችሁ…እዚህ ደረጃ ልንደርስ ምንም አልቀረን፡፡ በፊት ስልጣኔ ተብሎ… አለ አይደል…እነ ብሪቱ… ብሪትኒ፣ እነ በሪሁን…ብራድ ሲባሉ “ጉድ ነሽ የአንኮበር ቅጠል…” እንል ነበር፡፡ እንደ ዘንድሮ ነገረ ሥራችን ግን “ብሪቱ” ተብሎ ‘አንድ ቡድን’ ውስጥ ከመደልደል “ብሪትኒ” ተብሎ “አልቀረብሽም…” መባሉ ሳይሻል አይቀርም፡፡ አለ አይደል… ብሪትኒ “የኔኦ ሊበራሊስቶች ናፋቂ ነች…” ምናምን ካልተባለ! ቂ…ቂ…ቂ… አሀ…በዚች በሚወጣው ደረጃ ሁሉ አጃቢ ሆና የቀረችው አገራችን ውስጥ የማይሆን ነገር የለማ!
እናላችሁ… “ሆቺ ሚን እበላለሁ…” ብትሉ በቃ ቶሎ ተብሎ “ይሄማ ቅልጥ ያለው ኮሚኒስት ነው…” ምናምን ልትባሉ ትችላላችሁ፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የስም ነገር ካነሳን አይቀር እዚቹ የእኛዋ የዓለም ክፍል እየተበላሹ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ታዲያላችሁ…ሰዎች በስማቸው የተነሳ የአገልገሎት ቅድሚያ የሚያገኙበት፣ ወይንም ጭርሱን “ከሁለት ሳምንት በኋላ ተመለስ…” የሚባሉበት ነገር በየቦታው አለ ይባላል፡፡
የምር እኮ… አንዳንዴ ችሎታና ብቃቱ ኖሮ እንኳን በስም የተነሳ የሥራ ዕድል ሊያመልጥ ይችላል፡፡ አንድ ሰሞን በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች አገልግሎት ለማግኘት እስከ አያት ድረስ ስም ይጠየቅ ነበር፡፡ “በአባት ቢሸውደን በአያት ያዝነው”… አይነት ነገር ነዋ!
 የስም ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…አንድ ቀን ጠዋት ሰውየው ቁጭ ብሎ ጋዜጣ ያነባል፡፡ ድንገት ሳያስበው ሚስቱ ከኋላ ትመጣና በሆነ ነገር አናቱን ትለዋለች፡፡ እሱም ይደነግጥና “ሴትዮ ያምሻል እንዴ! ምን መሆንሽ ነው?” ይላል፡፡
እሷም ብጣሽ ወረቀት ታወጣላችሁና… “ይሄን ወረቀት ከኪስህ ውስጥ ነው ያገኘሁት” ትለዋለች፡፡
“እና ምን ይጠበስ!”
“ላዩ ላይ ሜሪ ተብሎ ተጽፏል፡፡ ሜሪ ማናት?”  
ይሄኔ እሱ ሆዬ ምን ይላል… “ለዚህ ነው እንዴ! ከሁለት ሳምንት በፊት ለፈረስ ውድድር መሄዴ ትዝ አይልሽም!”
“እናስ…!”
“ሜሪ እኮ እኔ የተወራረድኩባት ፈረስ ነች፡፡” ነገርዬው በዚህ ያልቃል፡፡
ከአንድ ሳምንት በኋላ እንዲሁ ቁጭ ብሎ ጋዜጣ ሲያነብ ሚስት ከኋላ አድብታ ትመጣና በመጥበሻ አናቱን ትለዋለች፡፡ እሱም “አሁን ደግሞ ምን ሆንሽ?” አላት፡፡
እሷዬዋ ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ፈረሷ ሜሪ ስልክ ላይ ትፈልግሀለች፡፡”  
የምር ይሄ የማይረባ ነው…ካልጠፋ ማመሳከሪያ በፈረስ ይወክላታል! እንደፈለገው…. አርባ አምስተኛ ታቦት ነሽ… ሊል ምንም የማይቀረው ሰውዬ መፋጠጥ ሲመጣ  “የተወረራደኩባት ፈረስ ነች…” ሲል አሪፍ አይደለም፡፡
እናላችሁ… የምር እንጋገር ከተባለ ‘ባህላዊ’ የምንላቸው ስሞች መጀመሪያ ስንሰማቸው የሚሰጠን ትርጉም አላቸው፡፡ ለምሳሌ ለሴቶች ከበቡሽ፣ የዓይኔ አበባ፣ ሁሉአገርሽ የሚባሉ ስሞች አሉላችሁ፡፡ (በሌሎች ቋንቋዎች ያሉትን ስለማላውቅ እንዳልዘባርቅ ብዬ ነው፣) ለወንዶች ደግሞ ባንትይርጉ፣ በአምላኩ፣ ደፋባቸው የሚሉ ስሞች አሉላችሁ፣ እነኚህ ስሞች በ‘አንበሳ ጎፈር’ አይነት የሚወጡ ሳይሆን በውስጣቸው የየራሳቸው ታሪኮች አሏቸው፡፡ እናማ…በአገራችን ስሞች ከመጽሔት ሽፋንና ከ‘ቦክስ ኦፊስ’ ዝርዝር የሚወጡ ሳይሆን የየራሳቸው ጥራዝ የሚወጣ ታሪከ ያላቸው ናቸው፡፡
እናማ…ይሄ ሁሉ ተረስቶ ስሞች የ‘ቦተሊካ ቡድን መደልደያ’ እንዲሁም የአገልግሎት ማግኛና መነፈጊያ ሲሆኑ በጣም ያሳዝናል፡፡ እናማ…መታወቂያ ምናምን ካልተባለ በስተቀር…አለ አይደል…ስምን ‘ለጠያቂው እንዲያመች’ አድርጎ መንገር የአገልግሎት ማግኛ ስትራቴጂ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእንደዚህ አይነት ዝቅጠት ይሰውረንማ!
ታዲያላችሁ…ስምም ሆነ ነገሮች ሁሉ ‘ለጠያቂው እንዲያመች’ ሆነው እንዲቀርቡ ማድረግ ልናስበው ከምንችለው በላይ እየተለመደ ያለ ነገር ነው፡፡ ምን ይደረግ…አለበላዛ ጦም ማደር ሊመጣ ነዋ!
ነገሮችን ‘ለጠያቂው እንዲያመች’ ስለማድረግ ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ በሶቪየት በኮሚኒዝም ዘመን የሆነ ነው አሉ፡፡ እናማ… የዶሮ እርባታዎች ተቆጣጣሪ የሆነ የመንግሥት ሰው እየዞረ የእርባታ ስፍራዎችን ይጎበኛል፡፡ ለእያንዳንዱ የዶሮ አርቢ አርሶ አደር አሥራ አምስት ሩብል ተሰጥቶት ነበር፡፡
ታዲያላችሁ… አንዱ አርሶ አደር ገንዘቡን እንዴት እንደተጠቀመበት ሲጠየቅ… “አምስቱን ሩብል የዶሮ … ገዛሁበት” አለ፡፡ ተቆጣጣሪውም አርሶ አደሩ ቀሪውን አሥር ሩብል ለራሱ አስቀርቷል በሚል እንዲታሰር ያደርገዋል፡፡
ይህንን የሰማ ሌላኛው ከእርሱ አጠገብ የነበረ አርሶ አደር ሲጠየቅ፣ አሥራ አምስቱንም ሩብል ለዶሮዎቹ ቀለብ ማዋሉን ተናገረ፡፡ ተቆጣጣሪውም “ይህ በጀትን ያለ ዕቅድ ማባከን ነው…” ይልና እንዲታሰር አደረገው፡፡
ሦስተኛው አርሶ አደር ሆዬ፤ እነኚህን ዜናዎች ሰምቶ ተቆጣጣሪውን ተዘጋጅቶ ይጠብቀዋል፡፡
“ከአሥራ አምስቱ ሩብል ለዶሮዎቹ ቀለብ ያዋልከው ምን ያህሉን ነው?” ሲል ተቆጣጣሪው ጠየቀ፡፡ አርሶ አደሩ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ… “እኔ አሥራ አምስቱን ሩብል ለዶሮዎቹ ነው የምሰጣቸው፡ እነሱ ናቸው የፈለጉትን የሚያደርጉበት፡፡” አሪፍ አይደል!
እናማ…ስማችን ‘ላም ባልዋለችበት ኩበት የምንለቅም’ የሚያስመስለን ከሆነ በምንጠራበት ጊዜ… “የማርያም ብቅል እፈጫለሁ…” የማንልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ አሀ…ከስም ጥሪው ጀርባ ‘የቦተሊካ ጋኔን’ ሊኖር ይችላላ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ጐመን መመገብ የጡት ካንሰርን ይከላከላል
የሳንባ ካንሰርን ለመከላከል አረንጓዴ አትክልቶችን ተመገቡ
የጨጓራ ህመምን ለማስታገስ የዝንጅብል ደንበኛ ሁኑ  

በምግብ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ልዩ ልዩ በሽታዎችን ለመቋቋም የሚያስችለንን አቅም ያዳብሩልናል፡፡ በዘርፉ የተለያዩ ምርምርና ጥናቶችን ያደረጉ ሳይንቲስቶች እንደሚገልፁት፤ በምግብ ውስጥ የሚገኙ ሚኒራሎችና ቫይታሚኖች የሰውነት በሽታ የመቋቋም አቅምን ያዳብራሉ፡፡ ቫይታሚኖችና ኢንዛየሞችን በብዛት ከያዙ የምግብ ዓይነቶች መካከልም በቤታካሮቲን የበለፀጉና የዚንክ ንጥረ ነገር ያላቸው ምግቦች እንዲሁም አረንጓዴ አትክልቶች፣ ነጭ ሽንኩርትና ፍራፍሬዎች ይገኙበታል፡፡ የምግቦች በሽታን የመከላከል አቅምና የመድሃኒት ፋይዳን በተመለከተ Journal of Medicine በመስከረም ወር 2013 እትሙ ካወጣው የጥናት ውጤት ጥቂቱን እናካፍላችኋለን፡፡
የሣምባ ካንሰርን የሚከላከሉ ምግቦች
በሣንባ ካንሰር ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ የአሜሪካ የካንሰር ኢንስቲቲዩት ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በየዕለቱ መመገብ ከሣንባ ካንሰር በሽታ ይታደጋል፡፡ ካሮት፣ ስፒናች፣ ብሮኮሊን፣ ሰላጣ፣ ቆስጣና ጐመን የሣንባ ካንሰር በሽታን አስቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ሣይስፋፋ ባለበት ለማቆም እጅግ ተመራጭ ምግቦች ናቸው፡፡ እንደተማራማሪዎቹ፤ አንድ ሰው በቀን አንድ ጊዜ እነዚህን ምግቦች ወይም ከእነዚህ ምግቦች አንዱን መመገብ ይገባዋል፡፡ ይህንን በማድረግም በሳምባ ካንሰር የመያዝ ዕድልን ከአምሳ በመቶ በላይ መቀነስ ይቻላል፡፡ እነዚህ አረንጓዴ አትክልቶች የሳንባ ካንሰርን ከመከላከልም ባሻገር በበሽታው ለተያዙ ሰዎች የበሽታውን ስርጭት በመቀነስ ዕድሜያቸውን ለማራዘም ይችላሉ፡፡
አትክልትና ፍራፍሬዎች በተፈጥሮአቸው ለካንሰር በሽታ መከሰት ምክንያት የሚሆኑ ኬሚካሎችን ከሰውነታችን ውስጥ የማስወገድ ብቃት ያላቸው ሲሆን በተለይ አረንጓዴና ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች የሳምባ ካንሰርን የመከላከል ብቃታቸው ከፍተኛ መሆኑንም ተመራማሪዎቹ ይገልፃሉ፡፡ በተለይም ቤታካሮቲን የተባሉ ንጥረ ነገሮችን በውስጣቸው የያዙ (ተክሎች የቢጫነት ቀለም እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ንጥረ ነገሮች ናቸው) የሳምባ ካንሰርን የመከላከል ብቃታቸው የላቀ ነው፡፡ የአትክልቶቹ ቀለም በደመቀ ቁጥር ከፍተኛ የቤተካሮቲን ንጥረ ነገሮችን የሚይዙ ሲሆን ይህም ለሣምባ ካንሰር አጋላጭ የሆኑ ኬሚካሎች ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ወደማይጐዳ ኬሚካልነት ለመቀየር ያስችላቸዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ እንደሚናገሩት፤ አንድ ሰው በሣምንት ውስጥ 140 ግራም የሚመዝኑ ሁለት ጥሬ ካሮቶችን ለሁለት ቀናት ቢመገብ፣ ስልሣ በመቶ በሳምባ ካንሰር የመያዝ ዕድሉን ይቀንሳል ጥሬ ስፒናችን በተመሳሳይ ሁኔታ ቢመገብ ደግሞ አርባ በመቶ በሣምባ ካንሰር የመያዝ ዕድሉን እንደሚቀንስ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
የሣንባ ካንሰር በሽታን የሚከላከለው ሌላ የምግብ አይነት ደግሞ እርጐ ሲሆን ለሳንባ ካንሰር የመጋለጥ እድልን በአንድ ሶስተኛ ይቀንሳል ተብሏል፡፡
የጡት ካንሰርን የሚከላከሉ ምግቦች
ለጡት ካንሰር እንዲሁም ለዩትሪንና ኦቫሪያን ካንሰር መከሰት ዋነኛው ምክንያት ለሴቶች የሴትነት ባህርይን የሚያላብሰው “አስትሮጂን” የተባለው ሆርሞን መዛባት ወይም በዝቶ መገኘት ነው፡፡ የዚህን ሆርሞን ብዛት የማስተካከል ብቃት ያላቸው ምግቦችን በመመገብ ችግሩ እንዳይፈጠር ለመከላከል እንደሚቻል የሚጠቀሙት ሳይንቲስቶቹ፤ የጡት ካንሰርን ለመከላከልና ሥርጭቱን ለመግታት ከሚታዘዘው “ታሞክሲፈን” የተባለ መድሃኒት በተሻለ በደም ውስጥ የሚገኘውን የአስትሮጂን መጠን የሚቀንሱ ምግቦች እንዳሉ ይገልፃሉ፡፡ አረንጓዴ ተክሎች (ጐመንና የጐመን ዝርያ ያላቸው ምግቦች) ለጡት ካንሰር በሽታ መነሻ ምክንያት የሆነውን የአስትሮጂን መጠን መብዛት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳሉ፡፡ በየዕለቱ በጥቂቱ የበሰሉ ወይም ጥሬ የጐመን ዝርያዎችን መመገብ በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ እንደ ተመራማሪዎቹ፤ ስንዴ በጡት ካንሰር የመያዝ አጋጣሚን ከሚቀንሱ ምግቦች መካከል አንዱ ሲሆን በየዕለቱ 50 ግራም ያልበሰለ ስንዴ መመገብ ከፍተኛ ውጤት ያስገኛል። ባቄላ፣ አኩሪ አተርና፣ ሽንብራም በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልን ከሚቀንሱ ምግቦች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሥጋ፣ የበቆሎ ዘይት (corn oil) እና ከፍተኛ ስብነት ያላቸው ምግቦች ደግሞ የጡት ካንሰርን እንደሚያባብሱ ሣይንቲስቶቹ ይናገራሉ፡፡
የጨጓራ በሽታን የሚያስታግሱ ምግቦች
የጨጓራ አሲድ መብዛትን ተከትሎ የሚመጣውን የጨጓራ ህመም ለማስታገስ ዝንጅብል እጅግ ተመራጭ እንደሆነ የሚጠቁመው የተመራማሪዎቹ ጥናት፤ በተለይ በጨጓራ ህመም ሳቢያ ለሚከሰት ማቅለሽለሽና ማስመለስ፣ የምግብ ፍላጐት ማጣትና የምግብ አለመፈጨት ችግር ፍቱን መድሃኒት ነው ብሏል፡፡
ሌላው በጨጓራ ህመም ለሚሰቃዩ ሰዎች የተጠቆመው ምግብ ደግሞ ሙዝ ነው፡፡ ሳይንቲስቶቹ የሙዝ ደንበኛ ሁኑ ሲሉ ይመክራሉ። ለጨጓራ ህመም መባባስ ምክንያት ይሆናሉ ከሚሏቸው ምግቦች መካከልም ጐመን፣ የተጠበሱና ጨው የበዛባቸው ምግቦችና ወተት ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል፡፡  
ለጉንፋን፣ ለሣልና ለብሮንካይትስ
ጉሮሮዎን ሲከርክርዎ ወይንም አልታገስ ያለ ሣል ሲያስቸግርዎ አሊያም የብሮንካይትስ ችግር ካለብዎ የሚሰነፍጡና የሚያቃጥሉ እንደ ቃሪያ ያሉ ምግቦችን ይመገቡ፡፡ ነጭ ሽንኩርት ለእንደነዚህ አይነቶቹ ችግሮች ፍቱን መድሃኒት እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ይገልፃሉ፡፡ ነጭ ሽርኩርት  የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን ያስከትላሉ የሚባሉትን “ሪኒኖ ቫይረስ፣ ፓራ ኢንፈሌንዛና” የጉንፋን መነሻ የሆኑ ቫይረሶችን ዘጠና አምስት በመቶ እንደሚገድል ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ሰናፍጭ፣ ቃሪያና ሚጥሚጣ የአየር መተላለፊያ ቧንቧዎችን የሚዘጉ ንፍጥ መሳይ ፈሳሾች በፍጥነት በማቅጠን በቀላሉ እንዲወጡ ያደርጋሉ፡፡ 

Published in ዋናው ጤና

“ብዙ በሠራህ ቁጥር ጥቂት ትናገራለህ፡፡ ምክንያቱም ጥርት አርገህ ታውቀዋለህ፡፡”
ተፈራ አባተ የፋና የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ማህበር ሥራ አስኪያጅ፡፡

ኅዳር 30/2006 ዓ.ም፤ የቀጠለው ጉዞዬ ወደ ፋና የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ማህበር ነበር፡፡ ይህኛው ማህበርም የቀጠለው ጉዞዬ ወደ ፋና የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ማህበር ነበር፡፡ በዚህኛው የፋና ጽሕፈት ቤት ተረጋግተን ተቀምጠን ነው ውይይቴን የቀጠልኩት፡፡
 “ፋና እንዴት ተመሠረተ?” አልኩት፤ ሥራ አስኪያጁን፡፡
“ፋና የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ማህበር የተመሠረተው… የኢየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (የእህማልድ) እዚህ ቀበሌ 12 ውስጥ ይሠራ ነበር - በ4 ፕሮግራም ላይ ይሠራ ነበር፡፡
ማለት 1) እናት አባት ያጡ ህፃናት 2) ጤና 3) ትምህርት 4) ኑሮ ማሻሻያ
እየሩሣሌም አንድ 4 ዓመት ቆይቶ ሲወጣ፣ የጀመረውን እኛ መልካም ሥራውን ተረከብን፡፡ ባጭሩ፤ ሥራውን የሚቀጥል ሰው መኖር ስላለበት ይሄ ማህበር እንዲመሠረት ሆነ፡፡ በማን? ብትለኝ፤ በቀበሌ 12 ማህበረሰብ ልማት መማክርት ከህብረተሰቡ የተመረጡ 72 የኮሚቴ አባላት ተገኙ፡፡ ሥ/አስኪያጅ ኮሚቴ ተመረጠ፡፡ ከዛ ከሥ/አ/ኮሚቴ ውስጥ ህዝቡ በሊቀመንበርነት መረጠኝ፡፡ ሁለተኛ ዙርም አሁን ተመርጬ ቀጠልኩ፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ ተሻሻለና በቦርድ እንዲመራ ሆነ፡፡ በቦርድ ሲመራም እኔ በሥራ አስኪያጅነት ተመረጥኩ፤ ተሾምኩ፡፡
ቀበሌያችን የችግርተኞች ቀበሌ ነው፡፡ ጄክዶም መጀመሪያ የገባው ይሄ ችግር በጣም የጠነከረ መሆኑን አስቀድሞ ተገንዝቦ ነው፡፡ አብዛኛው ቤተሰብ በእማ - ወራዎች ነው የሚመራው!” አለኝ፡፡
“ለመሆኑ ጄክዶ ወደ ህብረተሰቡ መጣ፣ ወይስ ህብረተሰቡ ወደ ጄክዶ መጣ?” ብዬ ጠየኩት፡፡
“ቆሻሻን የማስወገድ፣ የፅዳት ጉዳይ፤ ነበረ ዋና ሥራው፡፡ ወላጆች ያጡ ህፃናት በርካታ ናቸው፡፡ ዝቅተኛው ማህበረሰብ ይበዛል፡፡ ጄክዶ መጀመሪያ የህብረተሰቡን ችግር አይቶ እየተንቀሳቀሰ ነበር፡፡ እኛ ችግሩ አስጨንቆን በኋላ ነው ተሰብስበን ምን እናድርግ የተባባልነው፡፡
“ችግሩስ አሳሳቢ ነበር ያኔ?”
ዳኛቸው ተቀበለ ለምላሹ፡፡
“ይሄውልህ ትንሽ ዘርዘር አርገን እንየው!
በ1977 ዓ.ም ጄክዶ ህፃናትን በካምፕ ይዞ ያሳድግ ነበር፡፡ ከኮሙኒቲ ጋር መሥራት የጀመረው እኛጋ ነው፡፡ ትልቁ ሥራው፤ ማህበረሰቡ ችግሩን እንዲያወጣ አደረገ፡፡ ደረጃ አወጣ፡፡ 14 ፕሮግራሞች ነደፈ፡፡ 4 ፕሮግራም በአቶ ተፈራ አስተባባሪነት ለኛ ተሰጠ፡፡ ማህበረሰቡ ተረከበ፡፡ የቤት ኪራይ ነው ዋና ገቢያችን፡፡ አመራሩ በህብረተሰቡ ተመርጦ ነው፡፡ ሀብቱን የሚያንቀሳቀስው ራሱ ህብረተሰቡ ነው፡፡ ቤት ኪራይ አለ፡፡ ባለሀብቶች አሉን፡፡ ዘላቂነት ላልከው ይሄ ነው ጉዳዩ፡፡ የግሼ አባይ ቀበሌ ህዝብ 20ሺ ይሆናል፡፡”
“20ሺ ከሆነ ብዙኮ ነው፤ እንዴት approach ታረጉታላችሁ (እንዴት ትቀርቡታላችሁ)?” አልኩ ቀጥዬ፡፡
“ይሄ 3 ቀበሌ ነው፡፡ የ3 ቀበሌ ውሁድ ነው… ግሼ አባይ ነው እሚባለው፡፡ ሥራችን ህፃናቱን፣ ሴቱን፣ አረጋዊውን፣ መንከባከብ ነው እኛ አጋርም አለን፡፡ “ጐህ ለሁሉ” ነው የሚባለው፡፡ ያ ማህበር ይመለምላል፡፡ እኛ እዚህ ቀጠና ሶስት ሆነን በህፃናት ላይ እንሰራለን፡፡ 01፣ 02፣ 03 ቀበሌዎች፡፡ የህፃናት መምረጫ መስፈርታችን:-
1ኛ/እናትም አባትም 2ቱንም ያጡ
2ኛ/ ከእናት ወይ ከአባት አንዱን ብቻ ያጡ
3ኛ/ሌላ ሰው/ቤተሰብ የሚያሳድጋቸው
4ኛ/ ቤተሰብ ኖሯቸውም የተጐሣቆለ ህይወት ውስጥ ያሉ፤  
ፍፁም ችግርተኞችና ለችግር የተጋለጡ ናቸው፡፡
“ዘላቂነታችሁስ?” አልኳቸው፡፡
“የፋና ማህበር፤ ለጋሽ ባይኖርም ይኖራል! እዚህ ደረጃ ደርሷልና ሥጋት የለብንም አየህ፤ አንድ ፕሪንሲፕል አለው መርህ አውጥተናል፡፡ “አንድ ሰው አንድ አረጋዊ ይያዝ!” የሚል፡፡ ስኬታማ ነን! 38 ደጋፊዎች 38 አረጋዊ በሚገባ ተንከባክበዋል፡፡ እኛ facilitate (የማመቻቸት ሥራ)  ነው የምናረገው በዓል ሲኖር አርደን ቅርጫ እናከፋፍላለን! ሁልጊዜ! ነገሩ ምንድን ነው፤ መቼም እነዚህ ሰዎች ከጥሩ ኑሮ የወረዱ ናቸው፡፡ እነዚህን የመርዳት፣ የማቋቋም ጥሩ ኑሮ የማኖር፤ ሥራ ነው የሠራነው! የፌዴራል ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሠርተፊኬት የሸለመን ለዚህ ነው፡፡ ብቸኛ ተሸላሚ ነን!
ጄክዶ ዳሞ በልምድ ልውውጥ አኳያ ክህሎታችንን በጣም ቀይሮታል!
“ለሥልጠና ከዚህ ካላችሁበት ወጥታችሁ ታውቃላችሁ? ሌሎች ማህበራትን አይታችኋል?” አልኩ፡፡
“በመላው ኢትዮጵያ ለማለት ትችላለህ፡፡ ድሬዳዋ፣ ጅማ፣ አዋሳ፣ ደብረዘይት… ምኑ ቅጡ! ብዙ ቦታ ዞረን የሚጐድለንን ቀስመን መጥተናል!! የምናውቀውን አሳውቀናል!!
ከጄክዶም ውጪ Oxfam Canada ጋር ጅማ ሄደናል፡፡ ፋና ሠለጠነ ማለት ልምዱን ሥራ ላይ አዋለ ማለት ነው፡፡ ሥልጠና በፀጉር ሥራ፣ በምግብ ዝግጅት፣ በሹፍርና፣ ሞባይልና ጥገና
4000 ብር ለአንድ ሰው አውጥተን፤ ከዚያ በ6000 ብር ለአንድ ሰው አሳደግነው፡፡ 14 የሚሆኑ ሹፌሮች አሠልጥነን አውጥተናል፡፡
“ቮለንታሪዝም (የበጐ-ፈቃድ ሥራ) ከባድ ይመስለኛል፤ ለምን ቀጠለ?”
በሥራው ስለምንረካ ነዋ!” …  
አሁን ምንም የምትቀምሰው የሌላት፤ እንዲህ ቁጭ ብላ ሲያያት ሰው ያዘነ እንደሆን የቡና ቁርስ ይሰጣት የነበረች ምስኪን ሴት፤ አሁን ግን ብዙም ባይሆን 100-150 ብር ስታገኝ፣ የራሷን ህይወት እንደልቧ ስትኖር ማየት ያረካል፡፡  ሠፈር ወጣቱ፤ ጨርሶ ውሃ ልክ ላይ እንዳይቀመጥ ውሃ ልኩ ላይ የተቃጠለ የመኪና ዘይት፤ እየቀቡ እንዲሸሽ ይደረግ የነበረ ወጣት፣ ሙሉ በሙሉ ሰው ጠልቷቸው የነብሩ ልጆችን፤ አሰልጥነህ … ዛሬ መኪናውን ሲያሽከረክር ስታየው…ይሄን ባልደረባችንን ዳኛቸውን፤ ጋሼ ሠርቪስ ልስጥህ?” ሲለው ስታይ፤ ቤቱ ቅርብ ቢሆንም ሲወስደው ስታይ፣ በበጐ ፈቃደኝነት መሥራትህ እርክት ያረግሃል!
እንደዛ የሚሉ ልጆችን ማግኘት በሆቴል በምግብም ደረጃ ቤተሰቦቻቸውን የለወጡ፤ የተዛባ ኑሮ የነበራቸውን ሰዎች ያቃኑ ማየት፣ እንዴት ልዩ ደስታ አይሰጥህም፤ በፓፒረስ ሆቴል ተቀጥረው ታያለህ፡፡ ቤተሰቦቻቸውን የለወጡ ወጣቶች፡፡ እንዲህ ያሉ ወጣቶችን ማግኘት ትልቅ ፀጋ ነው! በቃ ትረካለህ! ቀለብህ እሱ ነው! ሌላ ደሞዝ የለህም!
የበጐ ፈቃደኝነት ሚሥጥሩ ይሄው ነው!”
ዳኛቸው ገባበት፡-  
“አንድ ተቋም የራሱን ሪሶርስ ካየ Sustain ያደርጋል-ዘላቂነቱን ያውቃል፡፡ ከፈረንጅ የሚጠብቅ ነው Sustain ላያረግ የሚችል፡፡ የራስን ሀብት ማፈላለጊያ መንገድ ማግኘት ነው ዋናው! እኛ ጄክዶ መሠረት አሲዞናል፡፡ አሁን ደሞ ጤፍ አምጥተናል፡፡ በ4 ወር ውስጥ ቢያንስ አሥራ ምናምን ሺ ብር አትርፈናል፡፡ ህብረተሰቡ በአያያዛችን በጣም ከመተማመኑ የተነሳ፤
“እንዲህ ላሉ ህፃናት ማገልገል እፈልጋለሁ” የሚል ማህበረሰብ እያፈራን ነው፡፡ የራሱ ሥራ ባለቤት ማምጣት ደረጃ ላይ ነው!
ብዙ ዘመን አብረን ኖረናል፡፡ ለ2ኛ ጊዜ ተመርጠናል፡፡ ከጄክዶ ጋር መሥራት ችለናል፡፡ ደከመኝ ሰለቸኝ አለማለት መቻላችንም ቀላል አይመስለኝም፡፡”
አቶ  ተፈራ ቀጠሉና “ይሄን ለመረዳት ባለክሊኒኮች አሉ፡፡ የነሱን በጐ አድራጐት እይ፡፡ እናንተ ብዙ ልጆች ትረዳላችሁ እኔ ግን 10 ህፃናት በዓመት ባክም ምን አለበት?” ያለን ባለ ክሊኒክ አለ፡፡
“ኧረ ይበዛብሃል አትችለውም?” ብንል፤
“ህፃናቱ በዓመት አንዳንዴኮ ነው የሚታመሙት፤ ምንም ሊያሳስባችሁ አይገባም’ ነው ያለን- በሙሉ ልብ!”
አረጋውያንን ምን እንደምናደርግ ቸግሮን ባለበት ሰዓት ከደብረዘይት ተማርን - ሬክሰን ከሚባል ድርጅት ጋር፡፡ ውይይታችን አበቃ፡፡
የፋና ማህበር ልበ - ሙሉነት አርክቶኝ ነበር የተለያየነው፡፡
በልቤ . ከመሠረቱ የጠና ማኅበር እስከመጨረሻው ሊጓዝ መቻሉን፤
በማህበረሰባዊ ልማት ለረዥም ዓመታት መቆየት እንዴት ልምድ - ጠገብ እንደሚያደርግ
ሰው ከሰው ተገናኝቶ፣ ተወያይቶ፣ ልብ ለልብ ተገናኝቶ እንዴት የልቡን ማድረግ እንደሚችል፤
በማህበረሰቡ ላይ ዕምነት ማዳበር እንዴት ወሳኝ እንደሆነና
ሌሎች እድሮችን ማቀፍ እንዴት ዘርፈ-ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚያስተምር፤ አሰብኩ፡፡ ከፋና የተማርኩት አመረቃኝ፡፡
ነገ ወደ አውራምባ ልሄድ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ልሄድ አቅጄ ያልሄድኩበት ቦታ ነው፡፡ አሁን ሊሣካልኝ ነው መሰለኝ፡፡ በጣም ጓጉቻለሁ!!
የባህር ዳርን ባህል ቤቶች ልጐበኝ ዞር ዞር አልኩ፡፡ ብዙ አስደሳች ትውስታዎችን መዘገብኩ፡፡ ወደፊት በሰፊው እንደምጽፍባቸው አመንኩ፡፡
ሲመሻሽ ሆቴሌ ገብቼ፤ ፊቴን ወደ ዙምራ አዙሬ ተኛሁ!
(ጉዞዬ ወደ አውራምባ ይቀጥላል)

Published in ባህል

“የመተካካት ሂደት የዱላ ቅብብሎሽ ነው”
አቶ አያሌው ጐበዜ “ዱላውን” ለማነው ያቀበሉት?

እናንተ … የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነኝ የሚለው “CPJ” እና የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነኝ ባዩ “ሂዩማን ራይትስዎች” ከላያችን ላይ አንወርድም አሉን አይደል? (ከኢህአዴግና ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት ላይ ማለቴ እኮ ነው!) እኔማ ባለፈው የአፍሪካ ሚዲያ ፎረም ሲካሄድ… ሦስቱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት፤ በጋራ የሰጡትን “ዱላቀረሽ” መግለጫ መስማታቸው ስለማይቀር አርፈው ይቀመጣሉ ብዬ ነበር፡፡ ችግሩ ግን “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…” የሚለውን ተረት አያውቁትም!፡፡ አያችሁ … የመብት ተሟጋቾች እኮ ችኮ ናቸው፤ ነገር ከያዙ አይለቁም፡፡ መቼም መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት ሶስቱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት “የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ የለም” ማለታቸውን የመብት ተሟጋቾቹ መስማታቸው አይቀርም፡፡ ግን ምን ያደርጋል? ሰሞኑን CPJ ባወጣው ሪፖርት፤ ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያን ከ10 የዓለም አገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧል (ገፅታ ለማበላሸት እኮ ነው!)
ድሮም ኒዮሊበራሊስቶች ለጦቢያ ተኝተው አያውቁም! እኔ ግን ሳስበው… እንዲህ ካሉት “ጃይንት” ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ “ፒስ” ማውረድ ነው ተመራጩ፡፡  (“አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው” አለ መሐሙድ!)
ይኸውላችሁ…ኢህአዴግን ልማት ወጥሮ ይዞት ነው እንጂ CPJ ን ማሳመን አያቅተውም ነበር፡፡ ትዝ ይላችኋል …እነ IMF እና እና ዎርልድ ባንክ በባለሁለት ዲጂቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከመንግስት ጋር ሲወዛገቡ! ኢህአዴግ ነፍሴ ምን አደረገ? 10 ዓመት ቢፈጅበትም አሳመናቸው! አሁን የኢህአዴግን ዕድገት እኮ  አምነዋል፡፡ ከጋዜጠኞች ተሟጋቾቹም ሆነ ከሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ጋር ያለውንም ውዝግብ፤ ኢህአዴግ በውይይት ቢሞከረው ይሻላል ባይ ነኝ፡፡
እኔ የምለው…በመብራት፣ በውሃና በስልክ አገልግሎቶች አዲስ የተቆረቆርን አገር መሰልን አይደል? (ደቡብ ሱዳን እኮ ተሻለች!) ሰሞኑን በኢቴቪ የሰማሁት የውሃ ችግር ግን “የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ” የሚያሰኝ ነው፡፡ “ሰሜናዊቷ ኮከብ” እየተባለች በምትሞካሸው መቀሌ ከተማ 3 ወር ሙሉ ውሃ አልነበረም ተባለ፡፡ (አሁንስ የታለ?) የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢቴቪ ቅሬታቸውን ሲናገሩ፤ በውሃ እጦት ክፉኛ መሰቃየታቸውን ገልፀዋል፡፡ (ግን እንደኛ ሳይማረሩ!) እኔማ… የመቀሌ ውሃና ፍሳሽ መ/ቤት፤ ተዘግቶ ነው ብዬ ተወራርጄ ነበር፡፡ አስበሉኝ!  ወዲያው የመ/ቤቱ ሃላፊ በኢቴቪ ከች አሉ (አለማፈራቸው!) እናም “የውሃ እጥረቱ የተከሰተው ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ ነው” ብለው በቀላሉ ተገላገሉት (ይሄማ የተበላ ዕቁብ ነው!)
“ስኳር ለምን ጠፋ?”
“ገበሬው ስኳር መጠቀም ስለጀመረ!”
“መብራት ለምን ይቆራረጣል?”  
“የኢንዱስትሪ ዘርፉ ስላደገ!” እነዚህ ሁሉ ሰበቦች አሁን ፋሽናቸው አልፏል፡፡ (ሃላፊው አልሰሙማ!)
እንዴ… እነ መብራት ሃይልና የውሃና ፍሳሽ መ/ቤት ከተማውና ኢንዱስትሪው ሲያድግ የማንን ጐፈሬ እያበጠሩ ነበር? (አብረው አያድጉም እንዴ?) ወይስ የአገሪቱን ዕድገት እየተነበየ፣ ዕቅድ የሚያወጣ አዲስ መ/ቤት ማቋቋም ሊያስፈልግ ነው? (አሁንም እቅጯን ይናገሩ!)
እኔ ግን አንድ ሃሳብ አለኝ…ሦስቱ ትላልቅ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ውሃና ፍሳሽ፣ መብራት ሃይል፣ ኢትዮ - ቴሌኮም) የኢኮኖሚ ዕድገቱና የከተሞች መስፋፋት ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው፣ ትንሽ የዕድገቱ ግስጋሴ በረድ…ቀዝቀዝ … ቢልላቸው ጥሩ ነው (ሌላው ለጥጦ ያቅዳል እነሱ …) ይሄ እንግዲህ በቀና ልቦና ሲተነተን ነው፡፡ ግን ደግሞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት፤ የSabotage (አሻጥር) ነገር ሊኖርበትም ይችላል፡፡ ምናልባትም የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞች ሰርገው ገብተው ይሆናል፡፡ (መረጃ ውድ በሆነበት አገር ሃሜትና ጥርጣሬ ቢነግስ አይገርምም!)
እኔ የምለው ግን…አፄ ምኒልክ ድንገት ቀና ብለው ይሄን ሁሉ “ምስቅልቅል” ቢመለከቱ “የት አገር ነው የነቃሁት” ብለው ግር የሚላቸው አይመስላችሁም? ከአንድ ክ/ዘመን በኋላ ጦቢያን እንደ አውሮፓ ሆና አገኛታለሁ ሲሉ፣ ከጥንቱም ብሳ ሦስት ወር ውሃ የሚጠፋባት አጃኢብ አገር ሆናላቸዋለች (እንዴት እንደሚያፍሩብን!)
በነገራችሁ ላይ…ካዛንቺስ አካባቢ ባለገመዱ ስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ድፍን ወር ሞላው፡፡ ምኒልክ ቢኖሩ … “ማርያምን አልምርህም!” ይሉን ነበር፡፡ እናላችሁ…ኢትዮ ቴሌኮም በተደጋጋሚ ደውለን (በሞባይላችን ማለቴ ነው!) ስንጠይቅ የተሰጠን ምላሽ ምን መሰላችሁ? “አገልግሎቱ የተቋረጠው ከመንገድ ሥራው ጋር በተያያዘ ስለሆነ ትንሽ ታገሱ” የሚል ነው (ኧረ ተመስገን ነው! መዘለፍም አለ እኮ!) እኔ የምለው ግን… “ትንሽ ታገሱ” ሲባል ምን ማለት ነው? 1 ወር? (ወርማ ሊያልፈን ነው!) 2 ወር? 1 ዓመት? 5 ዓመት? (አልነገሩንማ!) ለጊዜው ግን እኛም የመንገድ ሥራ ማለት “ልማት” እንደሆነ ስለምናውቅ፣ የመንግስት ልማት ከሚስተጓጐል የእኛ ልማት አፈር ድሜ ይብላ ብለን ልንታገስ ተስማማን (ምርጫ የለንማ!) ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? የዛሬ ዓመት ገደማ የኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ ሃላፊ፤ ከኔትዎርክ ችግር ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የመንገዱን መቆፋፈር እንደምክንያት ሊያቀርቡ አሰቡና፣ የፓርቲያቸውን ግምገማ ፈሩ መሰለኝ፣ እንዲህ በብልሃት ተናገሩ:- “ከተማዋ ምስቅልቅል ላይ ናት…ግን የዕድገት ምስቅልቅል ነው!” (ከማንኛውም ምስቅልቅል ያውጣን!)
እኔ የምለው ግን … ይሄ ለሁሉ ነገር እንደ ፍቱን መድሃኒት የሚታዘዘው የ1ለ5 አደረጃጀት (በቤት ስሙ “ጥርነፋ!”) በቴሌ፣ በውሃና ፍሳሽ፣ እንዲሁም በመብራት ሃይል አልተሞከረም እንዴ? (1ለ5 ያልገባበት የለም ብዬ እኮ ነው!) በቅርቡ እንደውም ይሄ አደረጃጀት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መግባቱን የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩና የመድረክ ፓርቲ አመራር አባል የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ተናግረዋል (የአካዳሚ ነፃነት ውሃ በላው እንዴ?) ግን እኮ እዚህ እንደውም ዘግይቷል፡፡ በየክልሉ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች፣ የ1ለ5 አደረጃጀት ሥራ ላይ ተተግብሮ አመርቲ ውጤት እንዳመጣ፣ በኢቴቪ መስኮት ብቅ የሚሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እየመሰከሩ ነው (ካድሬ ናቸው እንዳትሉኝ!) ዝም ብዬ ሳስበው (መረጃ የለማ!) 1ለ5 ለተማሪዎች እንኳን ሳይበጅ አይቀርም (ለፖለቲካ ቅስቀሳ ሳይሆን ለጥናት!) ችግር የሚመጣው አንድ ፕሮፌሰር ከአምስት ዶክተር ጋር ይጠርነፍ ሲባል ነው (እዚህ አገር ፍሬን የለማ!) እናም በዚያው ከቀጠለ… አንድ ከፍተኛ ባለሃብት ከአምስት መካከለኛ ባለሃብቶች ጋር ይጠርነፍ መባሉ አይቀርም (ቀይ መስመር ማለፍ ተለምዶ የለ!)
ይሄን ፖለቲካዊ ወግ እየከተብኩ ሳለ፤ “ኢቴቪ ወዳጄ” … አንድ ሰበር ዜና ሹክ አለኝ፡፡ ለስምንት ዓመት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ያገለገሉት አቶ አያሌው ጐበዜ ባቀረቡት “የመተካካት ጥያቄ” መሰረት፣ አስቸኳይ ጉባኤ ተጠርቶ ሥልጣናቸውን ለምክትላቸው አስረከቡ አለኝ-ኢቴቪ! አይገርምም ፍጥነትና ቅልጥፍናቸው! የህዝብ አንገብጋቢ ጉዳዮችም አስቸኳይ ጉባኤ እየተጠራ እንዲህ አስቸኳይ እልባት ቢሰጣቸው አልኩ-በሃሳቤ፡፡ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ኢቴቪ ሌላ መረጃ አቀበለኝ፡፡ “የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሙሉ አምባሳደርነት ሹመት ተሰጣቸው” የሚል፡፡ ሌላ ፍጥነት! ሌላ ቅልጥፍና! አትሉም (ከሮቦት ብቻ የሚጠበቅ!) “የመተካካት ሂደት የዱላ ቅብብሎሽ ነው” ያሉት አቶ አያሌው ጐበዜ፤ “ዱላውን ለሚቀጥሉት ወጣት አመራሮች አስረክቤአለሁ” ብለዋል፡፡
እኔን ያልገባኝ ምን መሰላችሁ? የዱላ ቅብብሉ ዓይነት! (ወደ ጐን  የዱላ ቅብብሎሽ አለ እንዴ?) ሌላም ያልገባኝ ነገር አለ፡፡ ወጣቱ ትውልድ ወይም New blood የሚባለው የትኛው ነው? አቶ አያሌው ጐበዜን የተኩት (የቀድሞው ምክትላቸውን ማለቴ ነው!) የአዲሱ ትውልድ አባል ናቸው እንዴ? (“ለሚቀጥሉት ወጣት አመራሮች አስረክቤአለሁ” ስለተባለ እኮ ነው!) በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ New blood የሚለው በስንት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን እንደሆነ ግልፅልፅ አድርጐ ቢነግረን ከ“ብዥታ” እንወጣለን፡፡ ወይም ደግሞ የዱላ ቅብብሎሽ ወደ ጐንም ይቻላል ብሎ እቅጩን ይንገረን፡፡ ያኔ አፋችንን ዘግተን እንቀመጣለን (እኔ New blood እንዳልሆንኩ ይታወቅልኝ!)
በመጨረሻ … አንድ ጥያቄ አለኝ፡ አቶ አያሌው ጐበዜ ስልጣናቸውን የለቀቁበትን ምክንያት በፌስ ቡክ ላይ ይፃፉልን!! (“ኢህአዴግ ፌስቡክ መጠቀም ያበረታታል” ሲባል ሰምቼ እኮ ነው!!)

Monday, 23 December 2013 09:29

አቶ መለስ ከሞቱ ወዲህ

“ኢህአዴግ፣ በህልውና ስጋት ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ ገብቷል”
ጠ/ሚ ኃይለማርያም ቅን ናቸው፣ ነገር ግን ቅንነት ብቻውን በቂ ሊሆን አይችልም
ካለፈው ትውልድ ብንሻልም በሽታ አጋብቶብናል፤ አዲሱ ትውልድ ነው ተስፋዬ
በኢትዮጵያ የአረብ አገራት አይነት ቀውስ ከተፈጠረ ማብቂያ አይኖረውም”

ከኢዴፓ መስራችና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ልደቱ አያሌው ጋር የተደረገውን ቃለምልልስ ማጠቃለያ በዚህ ሁለተኛ ክፍል እናቀርባለን። የኢትዮጵያ ዋና ዋና ፈተናዎችን ከአረብ አገራት ቀውስ ጋር በማያያዝ፣ እንዲሁም ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት ወዲህ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ይተነትናሉ። በቅድሚያ ግን በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሁለት በሦስት ጥምረት ውስጥ የመሰባሰብ እድል አላቸው? ቀጣዩ ምርጫ አንድ አመት ብቻ ነው የቀረው…
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ አንድነት ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡ ችግሩ ግን በተቃዋሚ ጐራ ውስጥ የመቻቻል አዝማሚያ የለም፡፡ አንዳንዱ ታቃዋሚ ከሱ የተለየ አመለካከት የምታራምድ ከሆነ አሉባልታ ያስወራል፤ ጥላቻ ያራምዳል፡፡ ይሄ የሚያሳየው ከእኔ አመለካከትና መስመር ውጭ ማራመድ አይቻልም የሚል ስሜታዊ የፅንፍ አስተሳሰብ መያዙን ነው፡፡
በእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ደግሞ፣ መቻቻልን መፍጠር አይቻልም፡፡ በዚህ ረገድ በ2007 ዓ.ም ምርጫም ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡
ኢዴፓን በሚመለከት ፓርቲያችን ብቻውን ተዓምር ይፈጥራል የሚል እምነት የለኝም - የፓርላማና የክልል ምርጫ ላይ፡፡ ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብዬ የማምነው የ‹‹ሶስተኛ አማራጭ››ነት ሚናውን በማጉላት ነው፡፡ ምክንያታዊ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ምትክ የሌለው ምርጫ መሆኑን፤ እንዲሁም ገዢው ፓርቲና አብዛኛው የተቃዋሚ ጐራ እስካሁን የተጓዝንበት መንገድ እንደማይበጀን በማሳየት ረገድ ኢዴፓ ትልቅ ውጤት ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ በአግባቡ ከተጠቀምንበት፣ ሃሳባችንን ህብረተሰቡ ጋ ካደረስን፣ አጀንዳችንን በግልጽ ማስረዳት ከቻልን፣ የማይናቅ ውጤት እናመጣለን ብዬ አስባለሁ፡፡ የተወሰኑ መቀመጫዎችን ማሸነፍም እንችላለን፡፡
በእርግጥ የተወሰኑ ወንበሮችን ማግኘት በአገር አቀፍ ደረጃ ያን ያህል ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ዋናው ነገር አመለካከትን ማስተካከል ነው፡፡ ያኔ ዘላቂ ለውጥ ይመጣል፡፡ አብዛኛው ተቃዋሚና ገዢው ፓርቲ አሁን የያዙትን የሁለት ፅንፍ አመለካከት ይዘው እስከቀጠሉ ድረስ ግን፤ ኢዴፓ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው በተራዘመ ጊዜ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በህብረተሰቡ ውስጥ የኢዴፓን አመለካከት ለማስፋፋት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ብቻችንን ይሄን ውጤት በአጭር ጊዜ እናመጣለን የሚል አጉል ተስፋ የለኝም፡፡ አሁን አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች ኢዴፓ የያዘውን አመለካከትና አቀራረብ ቢቀበሉት ግን፤ ውጤቱ በጣም ፈጣን ይሆናል፡፡
እና ተቃዋሚዎች መሰባሰብ ቢችሉ ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ?
መሰባሰብ የሚያስፈልገው፤ ሰላሳ፤ አርባ ፓርቲ ብሎ ለመቁጠር አይደለም፡፡ የሚፈጠረው ስብስብ፣ ከቀድሞዎቹ ስህተቶች በደንብ የተማረ መሆን አለበት፡፡ ያለፉትን ስህተች ላለመድገም የተዘጋጀ መሆን አለበት፡፡ ዝም ብሎ መሰባሰብ ጥቅም የለውም፡፡
“የእስካሁኖቹ ስብስቦች ለምንድን ነው ውጤታማ ያልሆኑት? ህዝቡ የጣለባቸውን ተስፋ እውን ማድረግ ያልቻሉት ለምንድነው?” በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ከታሪክ መማር መቻል አለብን። አሁን ግን ለመማር ብዙም ጥረት አናይም፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የቀድሞው ቅንጅት ምንም ስህተት ሰርቷል ብለው አያምኑም፡፡ ትክክል ነበር ብለው ያምናሉ፡፡ ካለፈው ስህተት መማር አልቻሉም፡፡
የኢህአዴግ አባል፣ በጭፍን ድጋፍ ሁሉንም ስህተት በተቃዋሚዎች ላይ እንደሚያላክክ ሁሉ፣ እነዚህ ተቃዋሚዎችም በጭፍንነት ሁሉንም ስህተት በኢህአዴግ ላይ ወይም በሌላ አካል ላይ ይለጥፋሉ፡፡
በዚህ መልኩ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ያለምንም ጥርጥር የተቃዋሚዎች ህብረት አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን፣ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ሲባል እንጂ፣ ህብረት መፍጠር በራሱ ግብ አይደለም። ጥሩ ለውጥ ማምጣት ከፈለግን የቀድሞዎቹ ህብረቶች ለምን ውጤታማ እንዳልሆኑ ቁጭ ብለን ከምር መወያየትና መገምገም አለብን፡፡ ስህተቶችን ቁልጭ አድርገን አውጥተን እነዚህን ስህተቶች፣ “አንደግማቸውም፤ ተምረንባቸዋል” ብለን ልናስተካክላቸው ይገባል፡፡
“መድሎት” በተሰኘው መጽሐፍዎ ላይ፣ የአቶ መለስ አለመኖር የስልጣን ሽኩቻን ያመጣል ብለው ነበር፡፡ አሁንስ የእርሳቸው በህይወት አለመኖር፣ ምን አንደምታዎች ይኖሩታል? ገዢው ፓርቲ ውስጥ ክፍፍል አለ እየተባለ ይወራል፡፡ የርስዎ ስጋት እውን ይሆናል ይላሉ?
በ“መድሎት” ውስጥ በገለጽኩት ሃሳብ ዙሪያ፣ አሁን እሳቸው ከሞቱ በኋላስ ትክክል ነው ወይንስ አይደለም ብዬ ነገሮችን ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ ግምገማዬ ትክክል እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ ያኔ ያነሳሁት ጭብጥ፤ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ መቆየቱ ካልቀረ አቶ መለስ በስልጣን ላይ ቢቆዩ ይሻላል ወይስ አይሻልም የሚል ነው፡፡  
የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው የተሻለ አቅጣጫ ሊይዝ የሚችልበትን መስመር ለማየት አቶ መለስ ከሌሎቹ የኢህአዴግ አመራሮች የተሻለ እድል ነበራቸው፤ ፍላጐቱም ነበራቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢህአዴግ በስልጣን ላይ መቀጠሉ እስካልቀረ ድረስ፣ አቶ መለስ ቢኖሩ ይሻል ነበር ብዬ አምናለሁ። ያኔም ብየዋለሁ፡፡
ለምን ቢባል፤ አቶ መለስ እሳቸውን የሚተኩና ጐልተው የሚታዩ ሰዎችን ፈጥረዋል ወይ? እዚህ ላይ ድክመት ነበረባቸው ብዬ አምናለሁ። እንደማንኛውም አምባገነን መሪ፤ በራሳቸው ስር ከፍተኛ ስልጣን አሰባስበው ነበር፡፡ እሳቸው ብቻ ነበሩ የሚደመጡበት፡፡ ከመደመጥም አልፈው የሚመለኩበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ያ ሁኔታ አሁን የራሱ የሆነ ጉዳት አስከትሏል ብዬ አምናለሁ፡፡
የመልካም አስተዳደር እጦትንና ሙስናን በመዋጋት ደረጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዢው ፓርቲ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ መተካካቱ ችግር አላስከተለም ማለት ነው?
እኔ ይሄን ከምንም አልቆጥረውም፡፡ አቶ መለስ በህይወት ከነበሩበት ጊዜ የተለየ ነገር የለም። እሳቸው በነበሩበት ጊዜ አቶ ታምራት በሙስና ታስረው ነበር፡፡ ተመሳሳይ ዘመቻዎችም ታይተዋል። ሙስና የሚገታው በዚህ ዓይነት ዘመቻ አይደለም፡፡ በመሠረታዊ የአስተሳሰብና የአሠራር ለውጥ እንጂ፣ በሰሞነኛ ግርግርና ዘመቻ የሚፈታ ችግር አይደለም። ግርግር በሳቸውም ጊዜ አይተናል፤ አሁንም እያየን ነው፡፡
ይልቅስ፤ አሁን የተፈጠረ አዲስ ነገር ሌላ ነው። ከአቶ መለስ ሞት በኋላ፤ የፓርቲው የስልጣን እንብርት  የት እንደሆነ በግልጽ ወጥቶ አልታየም። አልለየለትም፡፡ ህዝቡ፤ እኛ ተቃዋሚዎች፤ የኢህአዴግ አባላትም ጭምር እቅጩን የሚያውቅ የለም፡፡ ኢህአዴግ እንደ አዲስ ድርጅት ስልጣንን እንደገና የማደላደልና ዘላቂ የማድረግ ሂደት (ፓወር ኮንሰልዴሽን) ውስጥ ነው የገባው፡፡
ኢህአዴግ እንደ አዲስ ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ መግባቱ የዲሞክራሲ ሂደቱን በጣም ይጐዳዋል፡፡  አቶ መለስ ባይሞቱ ኖሮ፣ የሚቀጥለው ምርጫ የተሻለ ለውጥ ይታይበት ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ግን ኢህአዴግ እንደዛ አይነት ለውጥ ለማስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የስልጣንና የሃይል ድልድሉ አልጠራም፡፡
አቶ መለስ በኢህአዴግ ውስጥ፣ ሃያልና ገናና የሆኑት ባለፉት አስር ዓመታት ነው፡፡ ከዛ በፊት ገናና አልነበሩም፡፡ እንደ አቶ መለስ በሁሉም የኢህአዴግ አመራርና አባላት ዘንድ ተደማጭነት ያለው ገናና ሰው እስኪፈጠር ብዙ ዓመታት ይወስዳል፡፡ እስከዚያው ኢህአዴግ ተደላድያለሁ ብሎ ስለማይተማመን የህልውና ጉዳይ የበለጠ ያሳስበዋል፡፡ ልፈረከስ እችላለሁ ብሎ ይሰጋል። ተቃዋሚዎች ቀዳዳ ተጠቅመው ያዳክሙኛል ያፈራርሱኛል ብሎ ይፈራል፡፡ ስጋቱና ፍርሃቱም፣ የበለጠ በሩን እንዲያጠብና እንዲዘጋ ይገፋፋዋል፡፡
ይህንን ነው እያየሁ ያለሁት፡፡ ከዛ አንፃር ነው፤ አቶ መለስ ቢኖሩ ይሻል ነበር የምለው፡፡ በመሪነት ሚናቸው አምባገነን ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን አቶ መለስ ዞሮ ዞሮ ያን ያህል ዓመት ገዝተውናል። የኋላ ኋላ ለታሪካቸውም ሲሉ፣ የመንግስት መሪ በመሆን ከተማሯቸው የተለያዩ ጉዳዮች በመነሳት፣ ከሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች በተሻለ መልኩ፣ በጐ ለውጥ የማምጣት እድል ነበራቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚያን እድሎች የመጠቀም አንዳንድ ምልክቶችም እያየን ነበር፡፡ በ97 ምርጫ፤ በሩን ሰፋ የማድረግ ሁኔታ ያየነውም  ከዛ ጋር የተያያዘ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት አምባገነን ነው፤ አቶ መለስም አምባገነን መሪ ነበሩ፤  ግን ከኢህአዴግ አመራር አባላት ውስጥ ማወዳደር ካስፈለገ፣ አቶ መለስ የተሻሉ ዲሞክራት ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ እሳቸው ከስልጣን ከመውረዳቸው በፊት ለተወሰኑ አመታት በስልጣን ቢቆዩ ለአገሪቱ በዲሞክራሲ ሂደቱ የተሻለ ነገር ሊያመጡ ይችላሉ የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ አሁን እሳቸው በህይወት የሉም፡፡ ኢህአዴግ በህልውና ስጋት ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ ገብቷል፡፡ በቀጣዩ አመት ምርጫ የተሻለ ነገር ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳይኖረኝ ያደረገኝ ይኼ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ዋና ዋና ፈተናዎችና ትልልቅ ስጋቶች ሶስቱን ይጥቀሱ ቢባሉ የትኞቹን ያስቀድማሉ?
አንደኛው ፈተና፣ የዲሞክራሲ ሂደት አለመኖር ነው፡፡ ዲሞክራሲ ታፍኖ በቀጠለ ቁጥር፣ አገሪቱ አደጋ ማስተናገዷ የማይቀር ነው፡፡ ዲሞክራሲን እስከወዲያኛው አፍኖ መኖር አይቻልም፡፡
የዲሞክራሲ ጥያቄዎች እንዳልተመለሱና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ እንዳልተከበሩ ህብረተሰቡ እሮሮ እያቀረበ ነው፡፡ ይሄ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ሁልጊዜ የህዝብን ጥያቄ ወይም የተቃዋሚን እንቅስቃሴ በሃይል እያፈኑ መኖር አይቻልም፡፡ እመቃውና አፈናው ያለ ምንም መሻሻል ከቀጠለ፣ ኢትዮጵያን ወደ መጥፎ አደጋ ሊያስገባት ይችላል፡፡ አንዱ ስጋቴ ይህ ነው፡፡
ሁለተኛው ከሙስና ጋር የተያያዘው ስጋት ነው፡፡ በስርዓቱ ውስጥ እጅና ጓንት ሆኖ አላግባብ የሚጠቀምና የኢኮኖሚ የበላይነትን የሚቆናጠጥ ማህበረሰብ እየተፈጠረ ነው፡፡ ብዙ ጦም አዳሪ ባለበት አገር፤ አንዳንድ ሰዎች ከመንግስት ጋር ባላቸው ግንኙነት፣ የአውሮፓና የአሜሪካ ዓይነት ኑሮ ሲፈጥሩ ህብረተሰቡ እየታዘበ ነው፡፡ ይሄ የፖለቲካውን ብሶት የበለጠ ተቀጣጣይ ያደርገዋል፡፡ በተለይ  እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ብሔረሰብ ባለባትና የፖለቲካ ቅራኔ በከረረባት አገር፣ እጅግ አስጊ ነው፡፡ መፍትሔ ካልተበጀለት በቀር፣ ለአገሪቱ ትልቅ አደጋ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ሶስተኛው ስጋት፣ ኢኮኖሚያችን ውስጥ ያለው ችግር ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጥያቄ፣ የድህነት ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ የሰላም ጥያቄ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጥያቄ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ የኢኮኖሚ እድገት የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ ይህች አገር ከሞላ ጐደል  የእርሻ አገር ናት፡፡ ከተማ ከገባን ደግሞ የሱቅና የቢሮ አገር ናት፡፡ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች አገር አይደለችም፤ መሆንም አልቻለችም፡፡ መዋቅራዊ ሽግግር ካልመጣ በቀር፤ የእስካሁን አመጣጧ ከፍተኛ አደጋ ላይ ያደርሳታል፡፡ ለምን ቢባል፤ በመዋቅራዊ ሽግግር ኢንዱስትሪ ካልተስፋፋ፣ ድህነት እጅግ ይባባሳል፣ የሰው ኑሮ ይበልጥኑ ይናጋል፡፡ ያለጥርጥርም፤ የፖለቲካ አለመረጋጋትን ያስከትላል፡፡
የዲሞክራሲ ሂደት አለመኖር፣ ከሙስና ጋር የተያያዘ የሃብት ሽሚያ አበጋዞች መፈጠር እና ከእርሻ በላይ የሚሄድ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር አለመኖር ናቸው ሶስቱ ትልልቅ የአገሪቱ ፈተናዎች። አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ የዚህች አገር ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡
አካባቢያዊ ጉዳዮችን ላንሳ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በአረብ አገራት የተፈጠረውን እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል? የግብፅና የሶርያ ወደ አልተጠበቀ አቅጣጫ ማምራት እንዴት ይመለከቱታል?
አሁን የጠቀስኳቸው ሶስቱ የአገራችን ችግሮች ካልተፈቱ፤ ኢትዮጵያም እንደዛ አይነት ቀውስ የምታስተናገድበት አደጋ ይኖራል፡፡ በግብጽ፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ ያየነው አይነት ቀውስ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢፈጠር፤ ውጤቱ ከእነሱም የከፋ አውዳሚ ሊሆን ይችላል፡፡ በአገራችን ውስጥ የሚታዩ ችግሮች፣ ብዙ አቀጣጣይ ነገሮችን ያቀፉ ናቸው፡፡ ስሜታዊ ሃይሎች በቀላሉ የሚያግለበልቧቸው የብሔረሰብ ጉዳዮች፣ እንዲሁም ፅንፍ ድረስ የተወጠሩ ጭፍን የፖለቲካ አስተሳሰቦች በበረከቱባት አገር ውስጥ ቀውስ ተጨምሮበት ምን ያህል ውድመት እንደሚፈጠር ለማሰብ ይከብዳል፡፡
ግብፅ ውስጥ፣ ጐዳና የወጣው ጦር ሰራዊትና ጐዳና የመጣው ወጣት፣ በሰላምታ ሲጨባበጥ አይተናል፡፡ ቀውሱን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ ባይችልም፤ ያረግበዋል፡፡ በኛ አገር ግን እንደዚያ አይነት ማርገቢያ ነገር የሚፈጠር አይመስለኝም፡፡ ቀውሱ ውስጥ ከገባን ማብቂያና መመለሻ የምናገኝ አይመስለኝም፡፡ መፍራትና መጠንቀቅ ያለብን፣ ይህቺ አገር ወደዛ ዓይነት ቀውስ እንዳትገባ ነው። አንዳንድ ሰዎች እንደዛ ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሚናፍቁ አውቃለሁ፡፡ ግን ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ ለማንኛችንም አይጠቅምም፡፡
አገራችንን እንወዳታለን ካልን፤ አገራችን ችግሯ ተፈቶ ወደተሻለ ውጤት እንድትሄድ ከፈለግን፤ የዚያ ዓይነት ቀውስና አብዮት እዚህ አገር ላይ መከሰት የለበትም፡፡ ስላልፈለግን አይመጣም ማለት አይደለም፡፡ ቀውስ እንዳይከሰት መመኘት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የአገራችንን ዋና ዋና ችግሮች ለመፍታት መጣደፍ አለብን፡፡ የዲሞክራሲ ሂደትን ማነቃቃት፤ በሙስና የሃብት ቅርምት መኳንንትን መግታት፣ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከዓባይ ጋር በተያያዘ፤ ከሱዳንና ግብጽ ጋር ያለው የፖለቲካ ግንኙነት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ሠላም ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ከቅርብ ጊዜ አንፃር ካየነው፤ ኢትዮጵያ የምትሠራው ግድብ፣ ሱዳንንና ግብጽን ይጠቅማቸዋል እንጂ አይጐዳቸውም፡፡ በዚህ ረገድ፣ መንግስት የሚያራምደው አቋም እውነት ነው ብዬ እቀበላለሁ፡፡ ግድቡ እንደማይጐዳቸው እነሱም አያጡትም፡፡ ግብፅ እና ሱዳን ከኢትዮጵያ በሚሄድ የአፈር ደለል ግድቦቻቸው እየሞላ በጣም እየተቸገሩ ነው፡፡ ይሄ ችግር ይቃለልላቸዋል - ኢትዮጵያ በምትሰራው ግድብ፡፡ በክረምት ወራት በጐርፍ ይጐዳሉ፤ በበጋ ወራት ደግሞ የውሃ እጥረት ይገጥማቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትሰራው ግድብ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት እንጂ ለመስኖ አይደለም፡፡ ውሃው የኤሌክትሪክ ተርባይኖችን እያሽከረከረ ወደ ሱዳንና ግብጽ አመቱን ሙሉ ሳያቋርጥ ይሄዳል፡፡ ከክረምቱ ጐርፍና ከበጋው የውሃ እጥረት እፎይ ይላሉ፡፡
ውሃው በትነት እንዳይባክን በማድረግም የኢትዮጵያ ግድብ ትልቅ ጥቅም ያስገኝላቸዋል፡፡ በዚያ ላይ ሱዳንና ግብጽ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ችግር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል የመጠቀም እድል ይኖራቸዋል። በአጭሩ ከኢትዮጵያ ግድብ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያገኙ አይጠፋቸውም፡፡ ስለዚህ ግድቡ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን እነሱንም ይጠቅማል በሚለው አቋም የዲፕሎማሲ ጥረትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡
ነገር ግን ስጋታቸውንም በጥልቀት ማጤን ይገባል፡፡ የእነሱ ዋነኛ ስጋት፤ ኢትዮጵያ ወደፊት በኢኮኖሚ ካደገችና እንዲህ  ትልቅ ፕሮጀክቶችን መስራት ከጀመረች ወዴት ያደርሰናል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ካደገች፣ ሌሎችንም ወንዞች የመገደብና ውሃውን የመጠቀም አቅሟ ከጨመረ ምን ይፈጠራል የሚል ነው ስጋታቸው፡፡
ስለዚህ በአንድ በኩል በውሃው የመጠቀም መብታችንን እንዲቀበሉ የምንፈልገውን ያህል የእነሱንም መብት እንደምንቀበልና ጉዳት የማድረስ ሃሳብ ፈጽሞ እንደማይኖረን በቅንነት ለማስረዳት መጣር አለብን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ መጠርጠርና መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ እንዳናድግ አንዳንድ የተንኮል ስራዎችን አይሰሩም ብሎ መሞኘት አይቻልም፡፡ ተንኮል  ሊሠሩ እንደሚችሉ በታሪክ እናውቃለን፡፡
ዲፕሎማሲያችንን ጤናማ ማድረግ ያስፈልጋል። የነሱንም በቅንነት ለማስተናገድ መሞከር ይገባል። ነገር ግን የዲፕሎማሲ ግንኙነት፣ ላይ ላዩ እንደሚታየው ሙሉ በሙሉ ጤናማ ነው ማለት አይደለም፡፡ ይህቺ አገር እንዳታድግ፤ ዘላቂ ሠላም አንዳይኖራት ግብጽ ብዙ ነገር ስትሰራ ኑራለች፡፡ አሁን ከግብጽ በኩል ከዚህ የተሻለ አስተሳሰብ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ ነገሮችን በጥርጣሬ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ግን ደግሞ ሁልጊዜ ነገሮችን በጥርጣሬ እያየን ግንኙነቱን ይበልጥ እንዲሻክር እድል መፍጠር የለብንም፡፡ በእኛ በኩል በጐ አመለካከት መያዝና ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለእነሱም መብት እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ፣ የዲፕሎማሲውን ሚዛን ጠብቆ መጫወት ያስፈልጋል፡፡
የአባይ ውሃን መጠቀምና ግድብ መገንባቱን በተመለከተ ደስተኛ ነኝ፤ እደግፋለሁ፡፡ ግን ግድቡ የኢህአዴግ ፕሮጀክት ወይም የአቶ መለስ ራዕይ ብቻ አይደለም፤ የሚሊዮኖች ራዕይ ነው። እንደ አንድ ዜጋ የሳቸውም ራዕይ ነው፡፡ ግን የትውልዶችም ራዕይ ነው፡፡ የእኔም እና የአንቺም ራዕይ ነው፤ የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ራዕይ ነው፡፡ ይሄን የትውልዶች ራዕይ ከአንዱ ፓርቲ ወይም ከሌላኛው ድርጅት ጋር ሳናገናኝ ሁላችንም መደገፍ መቻል አለብን፡፡
በእኔ እና በእርስዎ ትውልድ ምን ዓይነት ኢትዮጵያን አያለሁ ብለው ይገምታ?
የእኔ እና የአንቺ ትውልድ መሃል ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ወይ ከቀድሞዎቹ አልሆንም፡፡ ወይ ከመጪዎቹ አልሆንም፡፡ አስቸጋሪ ነው፡፡ ባለፉት ትውልዶች ዙሪያ የነበረ ድክመት በተወሰነ ደረጃ ተጋብቶብናል፡፡ ነገር ግን ከእነሱ የተሻለ በጐ ነገር አለን ብዬ አምናለሁ፡፡ መሃል ላይ ነን፤  ነገር ግን ለመጪው ጥሩ ዘመን የሚመጥን ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡
ለዚች አገር የበለጠ በጐ ነገር የምጠብቀው፤ ከእኔ እና ከአንቺ ትውልድ ሳይሆን፤ ከእኛ በታች ካለው ትውልድ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲ፣ በኮሌጅ፣ በሃይስኩል ደረጃ ያለው ትውልድ ነው፤ የዚህችን አገር እጣ ፈንታ በዘላቂነት የሚለውጠው፡፡
ቀደም ሲል በፊውዳል ስርዓት፣ ከዚያ ቀጥሎም የግራ ፖለቲካውና የደርግ አገዛዝ የተፈራረቀባቸው ትውልዶችን አይተናል፡፡ ለዘመናት የዘለቀው ነባር ባህልና አስተሳሰብ ሁሉ የራሱ ችግር አለበት፡፡ ውጥንቅጥ  ውስጥ እንድንገባ ያደረጉንም እነዚህ ነገሮች ናቸው፡፡ በተለይ የግራ ፖለቲካ (ማርክሲዝም ሌኒኒዝም) ኢትዮጵያ ውስጥ መስፋፋቱና በደርግ አማካኝነት ለአስራ ሰባት ዓመት መንሰራፋቱ ብዙ የትውልድ አባላትን በክሏል፡፡ ከዚያ በሽታ ዛሬም አልተላቀቀንም፡፡ ከመቻቻልና ከመደማመጥ የተራራቅነው ያለምክንያት አይደለም፡፡ የተበላሸ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ስለኖርን ነው፡፡ ያ በሽታ በተወሰነ ደረጃ በእኔ እና በአንቺ ትውልድም ይታያል - ከቀድሞው ትውልድ ብንሻልም፡፡
ከኛ በታች ያለው  ትውልድ ግን ከበሽታ ነፃ የመሆን ዕድል አለው፡፡ ከመተላለቅና ከመጠላለፍ ይልቅ ነገሮችን በቀጥታ ለማየት የተዘጋጀ፣ ከቂም በቀል የፀዳ፤ ኮተት ያልተጫነበት ትውልድ እየመጣ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  የእኛ ትውልድ ከቀድሞው ትውልድ የተጋባብን የበሽታ ቅሪት ወደ አዲሱ ትውልድ እንዳይሻገር በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የኛ ትውልድ ሚና ይሄ ይመስለኛል፡፡ በውርስ የመጡ በጐ ያልሆኑ ነገሮች ይሄኛው ትውልድ ላይ መቆም አለባቸው፡፡
በጐ ያልሆኑት ነገሮች ስህተት መሆናቸውን በጉልህ አውጥተን በማስተማርና ጥሩ ጥሩ ነገሮችን በማውረስ አቅጣጫውን ማሳየት ይጠበቅብናል ብዬ አስባለሁ፡፡
የጠ/ሚ አቶ ሃይለማርያምና የአዲሱ አስተዳደር አዝማሚያና ብቃት ላይ ምን ይላሉ?
አዲሱን ጠ/ሚኒስትር በግል አውቃቸዋለሁ። ፓርላማ በነበርኩበት ጊዜ እሳቸውን የማግኘትና የማናገር ብዙ እድሎች ነበሩን፡፡ በጣም በጐና ቅን ሰው እንደሆኑ በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ ቅንነት ብቻውን በቂ አይደለም ግን በጐ ሰው መሆናቸው፣ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃላፊነታቸው ላይ የሚኖረው ቦታና አገራዊ ፋይዳውን ስናይ የራሴ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ኢህአዴግ ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አቶ ሃይለማርያም የተሻለ ነገር ለማምጣት ምን ያህል እድል አላቸው የሚለው ነገር ግልጽ አይደለም፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ለውጥ ለማምጣት ምን ያህል ፍላጐት አላቸው? ፍላጐትስ ካላቸው ምን ያህል አቅም አላቸው? አንድ መሪ በአንድ ድርጅት ወይም መዋቅር ውስጥ በአንድ ጊዜ ተደማጭነት የማግኘት እድል የለውም፡፡ ጊዜና ሂደት ይጠይቃል።
አቶ ኃይለማርያም ያንን ጊዜና ሂደት ቢያገኙ፤ የለውጥ ሃዋርያ ሆነው የተሻለ ነገር ይፈጥራሉ ወይ የሚለው ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ እድሉን ሳያገኙ ስልጣናቸውን ሊለቁ ይችላሉ ወይም እድሉን አግኝተው የተሻለ ሁኔታ ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆናል። ወይም እድሉን ላይጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ለጊዜው በርግጠኝነት መናገር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ትንሽ ጊዜ መጠበቅና ማየት ይሻላል፡፡  

Page 6 of 16