መግቢያ
ከ”የኢትዮጵያ ኮከብ” መፅሐፍ ደራሲ ከአብነት ስሜ ጋር ያለን እውቂያ ከሁለት አስርታት ይልቃል። በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ - ፅሁፍ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪያችንን አብረን ስንማር ጀምሮ እንተዋወቃለን፡፡ ይህንን መጽሐፍም ሳውቀው ያንኑ ያህል ጊዜ የቆየ ይመስለኛል፡፡ አሁን ባለው መልኩ ባይሆንም። በመጽሐፉ በተነሱ በርካታ ርእሰ ነገሮች ዙሪያ ያኔም እንወያይ ነበረና፡፡
ከደራሲው ጋር ከአንድ እጅ ጣቶች ላልበለጡ አመታት ተለያይተን ቆይተን ዳግም በተገናኘንበት አጋጣሚ የህትመት ብርሃን ያየውን ይህን መጽሐፍ “የእንኳን ደህና መጣህ” ገፀ በረከት ሆኖ እንደቀረበልኝ ስለሚሰማኝ ጭምር ነው መጽሐፉን ሳነበውና አንብቤ እንደጨረስኩ ስላሳደረብኝ ስሜት ጥቂት ልል የወደድኩት፡፡
በመጀመሪያ ግን በርዕሴ “ድፍረት፣ ጥልቀትና ቁጥብነት” የደራሲው መገለጫዎች ናቸው፤ ስል ምን ማለት ፈልጌ እንደሆነ ትንሽ ላብራራ፡፡ ድፍረት ስል፡- ሌሎቻችን ዳር ዳር ብለን የምናልፋቸውን ጥያቄዎች መጠየቅንና አጥብቆ መመርመርን ብቻ ሳይሆን፤ ያገኘውን መልስም ወይም የጥያቄዎቹን መልስ አልቦነት አፍን ሞልቶ መናገር መቻልን ማለቴ ሲሆን፣ ጥልቀት ስል ደግሞ፤ የሚያነሳውን ርዕሰ ነገር ከሁሉም ማዕዘናት አኳያ ብትንትን አድርጐ የማየትንና ለሌሎችም የማሳየት አቅምን ማለቴ ነው።
ቁጥብነትም ይህንን በድፍረት የተነሳውን ርዕስና በርዕሱ ዙሪያ ከሰፊ ንባብና ልምድ ተፈልፍለው፣ ነጥረው የወጡ አያሌ ሀሳቦችን ክሽን አድርጐ፣ አሳጥሮና አጣፍጦ የማቅረብ አቅምን ማለቴ ነው፡፡

ድፍረት
ለአንድ ህፃን “ፈጣሪ ሰማይና ምድርን፤ እንስሳትን፣ እፅዋትንና እኛንም ፈጠረ” ብለን ብንነግረው፤ “የት ጋ ቆሞ? ከምንና እንዴት? ለምንስ ፈጠረን? እሱንስ ማን ፈጠረው?” ወዘተ…እያለ፤ እኛ አዋቂ ተብዬዎች በቸልታም በሉት በፍርሃት የማናነሳቸውን፣ ግን ሊነሱ የሚገባቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ይጠይቃል፤ የሚመጣውን መልስም ሳይፈራና ለመልሱም ሳይጨነቅ ያን ድፍረት አብነት ውስጥ አውቀዋለሁ፡፡ ያን ድፍረት በመጋራቴም ብዙ ብዙ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ይህንን መጽሐፉን ያነበበም ሰው ያን ጠቀሜታ እንደማያጣ እተማመናለሁ፡፡
በተማሪነት ዘመናችን ዘወትር እያነሳን ከምንወያይባቸው በርካታ የፍልስፍናም ሆነ ስነ - ፅሁፍ ነክ ርዕሰ ጉዳዮቻችን መካከል አስትሮሎጂ አንዱ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ የኮከብ ትንተና ስለሰው ባህርይ ምን ያህል በትክክል ይነግረናል? መጠሪያ ስምስ ስለ ግለሰቡ ባህርይ ምን ይናገራል? የፊት ገጽታና የሰው ባህርይስ ምን ያህል ይዛመዳሉ? ሰውና አረማመዱ፤ አለባበሱ፣ ያሳደገው ውሻና የሚነዳው መኪናስ? የመዳፋችን አሻራስ ስለ እኛ ምን ይነግረናል? … ወዘተ እያልን፤ እናነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችና መልስ ፍለጋ ይነበቡ የነበሩ መፃህፍትም አይዘነጉኝም፡፡ ከዛም አለፍ ብለን፤ ነፍስ ባላቸው ልቦለዶቻችን ውስጥ ባሉ ገፀ-ባህርያት ዙሪያም መሰል ትንታኔዎችን የማድረግ ፍላጎቱና ሙከራውም ነበር። አብነትን ልዩ የሚያደርገው ግን፤ ከብዙዎቻችን በተለየ-አምርሮ በጥያቄው የመግፋት ድፍረቱና አጀንዳ አድርጎ የያዘውን ጉዳይ ከስር መሰረቱ ለመፈልፈልና መርምሮ ለመረዳት ያለው ትጋት ነው። ዛሬ ይህን መፅሀፍ ሳነብም የታየኝ የአብነት ድፍረት፤ በሌሎችም ምናልባትም በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ቢፅፍ የሚንፀባረቅ የአብነት መገለጫ፣ የማንነቱ አብነት ነው፡፡ ጠይቆ፣ ጠይቆ፣ ጠይቆ፣ መርምሮ፣ መርምሮ፣ መርምሮ፣ ያገኘውን መልስ፤ መልስ አልቦነቱንም ቢሆን፤ የደረሰበትን ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን፤ ለመናገርም ሆነ ለመፃፍ ኢምንት የማይፈራ መሆኑም ነው የአብነት ሌላው መገለጫ። ቢፈራ እንኳን መፍራቱን አፉን ሞልቶ በድፍረት ይገልፀዋል፡፡
አብነት በመፅሐፉ፣ አስትሮሎጂ “ሳይንስ ነው” ብሎ አስረግጦ ሲነግረን፤ ፍፁም ማመንታት ሳይታይበት ነው፡፡ አስትሮሎጂን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ማህበራዊ ሳይንሶች ከሚከተሉት የአጠናን ዘዴ ጋር በተያያዙ ውዝግቦች እንደ ሳይንስ ላለመቀበል ያለውን ክርክርም አጥቶት አይደለም በመፅሐፉ ውስጥ የሚለውን ያለን። እራሱ አንብቦ፣ መርምሮና ፈትኖ ሳይንስነቱን ቢያምን እንጂ። “አስትሮሎጂ ይሰራል፣ የሰዎችን ባህርይ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል” ሲለንም፤ በሙሉ ድፍረት ነው፡፡ ማወቅ ባስገኘለት ድፍረት፡፡ በኋላ ብመለስበትም፤ እንደ ወራት ሁሉ ዘመናትም ሀገራትም ኮከብ እንዳላቸው የሚያብራራበት መንገድም ድፍረትን አያጣም፡፡ የልቦለዱን ገፀ-ባህርይ የ“ፍቅር እስከ መቃብሩ”ን ጉዱ ካሳ፤ በአስትሮሎጂ ማዕቀፍ ውስጥ ሲተነትነውም ቢሆን … ለኔ የሚያምር ድፍረት ጎልቶ ይታየኛል፡፡ አብነት በድፍረትና በእርግጠኝነት ስለ አስትሮሎጂ ምንነትና ፋይዳ አስረግጦ የሚነግረን ለምን እንደሆነ ለማሳየት፣ በመፅሀፏ ገፅ አራት ላይ ያነሳትን እንደ ምሳሌ ላንሳና ወደሚቀጥሉት ነጥቦቼ ልሻገር፡፡ የአስትሮሎጂ አዋቂና አድናቂ የነበረው ኒውተን፤ አስትሮሎጂን አጣጥሎ በፊቱ ለተናገረ የስራ ባልደረባው የሰጠውን መልስ ደራሲው ይጠቅሳል፡- “ወዳጄ ሆይ፤ አንተ አስትሮሎጂን አላጠናህም፤ እውቀቱም የለህም። እኔ ግን አጥንቼዋለሁ፤ አውቀውማለሁ፡፡” ነበረ የኒውተን ምላሽ፡፡ አብነትም፤ ይሄ መልስ ውስጡ ያለውን፣ የልቡን ሀሳብ ስለወከለለት ሆን ብሎ የጠቀሰው ይመስለኛል። ሀሳቤን ይደግፉልኛል፣ ያጠናክሩልኛል ብሎ “እከሌ እንዳለው”ን መደጋገም ቀርቶ አንዴ እንኳን ማለቱን የማይመርጠው አብነት፤ ይህን ጥቅስ ሲጠቀመው ለሀሳቡ ትልቅነት በሰጠውን ዋጋ ምክንያት ይመስለኛል። በመፅሀፉ ውስጥ ዘርፉ ላይ  ያደረገውን ሰፊ ንባብና ምርምር ያህል በድፍረት የሚነግረንን እምነቱን ታላላቅ አንደበቶችን  በመጥቀስ (ወይም በመዘርዘር ልበለው) ተቀባይነትን ሲሻ አይታይም፡፡ ነጥቡን አስረግጦ ነግሮህ ውሳኔውን ላንተው ይተዋል እንጂ።
አስትሮሎጂ የሚያቀርበው ትንታኔ እውነት እንደሆነ የሚያረጋግጡ ጥቂት የማይባሉ የፍተሻ ጥናቶችን በተወሰኑ ምሳሌዎች ብቻ አመላክቶን ያልፋል፤ በመፅሀፉ ውስጥ፡፡ የአስትሮሎጂን ሀሳብ ውድቅ ለማድረግ ተነስቶ የሃያ ሺህ ሰዎች የልደት ሰንጠረዥ ላይ ቅኝት ያደረገው ታዋቂው የፈረንሳይ የስነ-ልቦና ባለሙያ ሚቸል ጎክሊን፤ በተገላቢጦሹ የአስትሮሎጂ ትንታኔ፤ ዘመናዊ የስነ-ልቦና ትንታኔ ከሚያስቀምጠው የሰው ልጆች የባህርይ ክፍፍል ጋር የተገጣጠመ መሆኑን ማረጋገጡንም፤ አብነት በመፅሀፉ (ገፅ 11) ላይ ይጠቅስልናል፡፡ ይህንን መሰል ብዙ ብዙ ማስረገጫዎችን አብነት እንደሚያውቅ አውቃለሁ፡፡ ሁሉን ግን አልፃፈልንም፤ አላሻውምና! ወይም ሌላው ዝርዝር የእሱ መገለጫ የሆነው ቁጥብነቱ ገድቦታልና፡፡ “በመላው ኮስሞስ ውስጥ መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥምረት አለ” ሲል የፃፈውን በዩኒክ ዩኒቨርስቲ የትወራዊ ፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆነው ሩዶልፍ ቶማስ ቼክን ሲጠቅስልንም፤ አብነት እራሱም በከዋክብቱ፣ ፕላኔቶቹና በእኛ፣ በሀገራችን፣ በዘመናችን፣ በጤናችን፣ በመካከላችን፣ በህልምና በእውናችን … በዘርፈ ብዙ የህይወት አላባዎቻችን መካከል አንድ አይነት መጣመር እንዳለ ማመኑን እየነገረን ይመስለኛል፡፡
ጥልቀት
ከነአባሪዎቹ ከ142 ገፆች ባልበለጠው በዚህ “ትንሽ” መፅሀፍ፤ በአስትሮሎጂ ማዕቀፍ ውስጥ ፀሃፊው ያነሳቸው ዘርፈ ብዙና ጥልቅ ሀሳቦችን በስሱ እንኳን ለመዳሰስ፤ እኔ አስር እጥፍ የሚበልጥ ዳጎስ ያለ መፅሀፍም ቢፃፍ ይበቃ አይመስለኝም፡፡ ተቆርጠው የቀሩ የሚመስሉና ተነካክተው የተተው ትልልቅ ጉዳዮችን እንኳን ትቼ፤ ዋና ዋና ነጥቦችን በወፍ በረር ብቃኝ፣ አብነት በመፅሀፉ ስለሚያነሳው ጉዳይ ምን ያህል በስፋትና በጥልቀት አብጠርጥሮ እንደፃፈልን ያሳያል ብዬ እገምታለሁ፡፡
የአኳሪየስ ኮከብ ዘመን በመግባቱ፤ አኳሪየስ ኮከብ ባላት አገራችን ላይ ያለውንና የሚኖረውን አንደምታ፤ በአስትሮሎጂ ማዕቀፍ ውስጥ መተንተንን ዋና የትኩረት ነጥቡ ባደረገው በዚህ መፅሀፍ፤ አዘጋጁ አስትሮሎጂን አስመልክቶ ያቀረበልን ማብራሪያ ስፋትና ጥልቀት ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በሚያጠግብና ሁሉም አጣጥሞ ሊያነበው በሚገባ ሁኔታ፡፡
ለዋናው ትንታኔ ዳራ ለመስጠት ሲል፣ ስለ አስትሮሎጂ ታሪካዊ አመጣጥና አሰራር በአስር  ገፆች ብቻ ያቀረበልን መረጃ እንኳን፣ እንደኔ-እንደኔ እራሱን የቻለ በርዕሱ ላይ የተፃፈ ዳጎስ ያለ መፅሀፍ ተነቦም የማይገኝ ጭብጥ ነው፡፡ ይህን ጥንታዊ የሆነ ጥበብ፤ ተጀመረ ተብሎ ከሚታሰብበት ከዛሬ ስድስት ሺህ አመታት ገደማ ጀምሮ ያለውን እድገቱን፤ እንደ ኃጢአት፣ አጉል እምነትና ወንጀል ተቆጥሮ አንቀላፍቶ ስለነበረበት ረዥም የጨለማ ጉዞ ጨምሮ ዳግም ልደቱንም አብነት ሲያወጋን፤ ከሰፊ ንባብ በተገኘና እጥር ምጥን ብሎ በቀረበ ገለፃ ነው፡፡ አይጠገቤው ሸጋ አቀራረቡ በዛ ላይ ተጨምሮበት፡፡
ብዙዎች የአስትሮሎጂ መፃህፍት፤ የአስትሮሎጂን ታሪክና አመጣጥ፣ ከግብፃውያን፣ ከከለዳውያን፣ ከሱሜራውያንና ሌሎች መሰል ጥንታዊ ስልጣኔዎች ጋር ብቻ አያይዘው መፃፋቸውንና ኢትዮጵያን አለመጥቀሳቸውን ቁጭት በተመላበት ድምፀት የሚገልፅልን ፀሃፊው፤ የኢትዮጵያችንን ከአስትሮሎጂ ጥበብ ጀማሪ አገሮች ተርታ ተሰላፊነት አስረግጦ ይነግረናል-ከጥንቃቄ ጋር፡፡ ምክንያቱም የነበሩንና ያሉንን እውቀቶች መርምሮ፣ ቆፍሮ አውጥቶ፣ በመረጃ አስደግፎ ለብርሃን ማብቃቱ ገና ብዙ ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ያውቃልና፡፡ (ከእንግዲህ እሱም አርፎ እንደማይተኛና ለዚሁ ስራ እንደሚተጋም አምናለሁ፡፡ የመፅሃፉ ዋና ትኩረት ባለመሆኑ ለጊዜው ነካክቶ ተወት ያድርገው እንጂ ነገ በሙሉ ልቡና አቅሙ እንደሚመለስበት በእምነትና በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡)
አልበርት ፓይክ በ1871 አሜሪካ ውስጥ አዘጋጅቶ ባሳተመው “ስነ-ምግባርና ቀኖና ለፍሪሜዚነሪዎች” በተሰኘ፤ ለዘመናት ምስጢራዊነቱን ጠብቆ ለዘለቀው ምስጢራዊ ድርጅት አባላት በሚሰጥ መፅሀፍ ውስጥ፤ የኢትዮጵያን ሀያል ሀገርነትና በስልጣኔም ከግብፅ ቀዳሚነት፤ ብሎም የብዙ ሚስጢራዊ ጥበቦች ባለቤት እንደነበረች የፃፈውን በዚህ መፅሀፉ ቀንጭቦ ያስነበበን አብነት፤ ሌሎችም ምሁራን የፃፏቸው መሰል ዘገባዎች እንዳሉ ያውቃል፤ ለጊዜው ዝርዝር ውስጥ አልገባም ብሎ ይለፈው እንጂ፡፡ ይህም ቁጥብነት ብዬ በርዕሴ ያመላከትኩት የአብነት ሌላኛው መገለጫ ነው፡፡
አብነት ስለ አስትሮሎጂ ታሪክና አመጣጥ ብቻ ሳይሆን ስለምንነቱና አሰራሩም፤ አጠር አድርጎ ነገር ግን አግዝፎ ባቀረበልን ገለፃ፤ በብዙዎች ዘንድ ስለ አስትሮሎጂ ያለውን የላይ ላዩን ግርድፍ ግንዛቤ ከፍ ባለ ደረጃ የሚያሳድግ ይመስለኛል፡፡ ፀሐይ፣ ጨረቃና ስምንቱ ፕላኔቶች በአስትሮሎጂ ትንታኔ ያላቸውን ፋይዳ ሲያስረዳን ብትንትን አድርጎ ነው፤ አብጠርጥሮና አሳምሮ፡፡ እነዚህ አካላት በህይወታችን ዙሪያ ያላቸውን ተፅእኖ በሳይንሳዊ መንገድ ለማብራራት የሚያደርገው ሙከራም ሳይዘነጋ፡፡ እንደ ምናልባትም በምሳሌ መልክ ብዙ ጊዜ ሰምተነው ሊሆን የሚችለውን፤ በብዙ አገሮች በተመዘገበ የስታትስቲክስ መረጃ፤ ጨረቃ ሙሉ በሆነች ጊዜ የወንጀል ቁጥር ተበራክቶ የመታየቱን ሁኔታና ሌሎችም አመልካች አብነቶች በመፅሃፉ ውስጥ ጠቀስ ጠቀስ ማድረጉም አልቀረም፡፡
በርካቶች ስለ አስትሮሎጂ ሲነሳ፤ እንደ ብቸኛው አጀንዳ አድርገው የሚመለከቱት የሚመስለኝ፤ “የእከሌ ኮከብ ሊዮ ነው፤ እከሊት ኮከቧ ሊብራ ነው” ሲባል ታሳቢ የሚደረገው የፀሐይ ምልክት (በተወለድንበት ወር ፀሐይ የገባችበት ከአስራ ሁለቱ የዘዲያክ ምልክቶች አንዱ የሆነው ዋና ኮከባችን) ከሃምሳ እስከ ሰባ በመቶ የሚሆነውን ባህርያችንን ብቻ የሚገልፅ መሆኑንና እንዲያውም እስከ 1930፣ በአስትሮሎጂ ጥናትና ልምምድ ይህ የፀሐይ ምልክት የሚባለው ነገር እንዳልነበረና የአንድን ሰው ኮከብም በዚህ መልኩ መስራት ከሙያ ውጭ እንደሆነ በማስረዳት፣ የተሟላ የባህርያችንን ትንታኔ ለማወቅ የልደት ሰንጠረዥን የመስራትን አስፈላጊነትና አሰራሩንም፤ ለዚህም የተወለድንበትን ዓመተ ምህረት፣ ወር፣ ቀንና ሰዓት እንዲሁም የተወለድንበትን አገርና ቦታ በማካተት፣ አንድ ሰው እንዴት የራሱ ብቻ የሆነ የኮከብ ትንታኔ እንደሚኖረው ይገልፅልናል፡፡ እንደ ፀሐይ ሁሉ ጨረቃና ሌሎቹ ፕላኔቶቹ በወቅቱ የነበሩበትን ሁኔታ ተመርኩዞ ስላለው የኮከብ ትንታኔ ግልፅልፅ አርጎ ያስረዳናል፡፡ ዝርዝሩን እኔ ባልነካካው እመርጣለሁ፡፡ በደፈናው ግን፤ አንድ ነገር ማለት የምችል ይመስለኛል፡፡ የአንባቢውን ግንዛቤ አስፍቶ፣ ስለ አስትሮሎጂም መሰረታዊ ዕውቀትን አስጨብጦ፣ ፋይዳና ጥቅሙንም ፍትፍት አድርጎ ማቅረቡ ለፀሃፊው የተሳካለት ይመስለኛል፡፡
የመፅሃፉ ዋና ክፍል የሆኑትን የአኳሪያስ ዘመን ትንታኔ (ስምንተኛው ሺህ በመባል የሚገለፀው)፣ ስለ ሀገራት ኮከብና የኢትዮጵያ ኮከብ አኳሪያስ መሆን ስላለው አንድምታ፤ ባማረ ሁኔታ ተከሽኖ የቀረበውን፤ አንባቢ እራሱ አንብቦ፣ አጣጥሞ እንዲደመምበት፣ እንዲማርበትና እራሱንም እንዲመለከተበት ከመተው ውጪ፤ በዚህች አጭር ፅሁፍ ልነካካውና አድበስብሼው ላልፍ አልመርጥም። ስለ ዘመናትና ስለ ሀገራት ኮከብ፣ ስለ አስትሮሎጂ ጥቅምና ምክሮቹ ቁልጭ አድርጎ የሚያቀርበው ትንታኔ፤ ለእኔ መፅሃፉን በማንበብ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡

ቁጥብነት
ባነሰቸው አንኳር ነጥቦች ዙሪያ ሁሉ ቆርጦ ያስቀረብን፤ ከዛም ይበልጥ የሚያውቀውና ያተወው  ብዙ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ይህም የአብነት ሌላው መገለጫ ነው። ቁጥብነቱን ያሳስበኛልና ስለዛ ጥቂት ልበል፡፡ ቁጥብነት የፀሃፊው መገለጫ ነው ስል፣ ሁለት አበይት ባህርያቱን ልጠቅስ ፈልጌ ነው፡- አብነት ላይ የማውቃቸውንና በ “ኢትዮጵያ ኮከብ” መፅሀፍ ላይም ያስተዋልኳቸው ናቸው፡፡
ደራሲውን ሳውቀው ጀምሮ ሲናገርም ሆነ ሲፅፍ፤ የቱንም ያህል ግዙፍና ውስብስብ፣ ረቂቅና ሰፊ በሚባል ሀሳብ ላይ ቢሆን፤ ቅልብጭና ጥርት አድርጎ ነው፡፡ ገና ብዙ ይላል ብለህ ስትጠብቀው፤ እሱ ግን የሚለውን ብሎ ጨርሷል፡፡ አብነት ግጥም ነው ብል (ያውም የሚጥም ቅኔ) ያጋነንኩ አይመስለኝም። የሚለው ነገር ኖሮ ያንን ሳይለው ቀርቶ ሳይሆን ሌሎቻችን ብዙ ብዙ ብለን የምንገልፀውን ሀሳብ፣ እሱ በአጭሩ አስውቦ ሊለው በመቻሉ ይመስለኛል። ምናልባትም ባለው ላቅ ያለ የቋንቋ ክህሎት እና ፈጣሪ በቸረው ፀጋ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
አብነት በመፅሀፉ መደምደሚያ ስለ ብሔራችን ኮከባችን ከፃፈው ጥቂት አቅርቤ ቅኝቴን ልቋጭ፡፡

ስለ ብሔራዊ ኮከባችን
አሁን የዘመን ዓይነጥላችን ተገፏል፡፡ ስለዚህ በደስታ መደናበርና በሐሴት መጨፈር ሳይሆን መንገዳችንን አጥርተን በመመልከት፣ በልዕልና ጎዳና ላይ በእርጋታና በልበ ሙሉነት መጓዝ ነው የሚጠበቅብን፡፡
አሁን እውቀትን እናክብራት፤ ጥበብንም እናንግሣት። ከስደትም እንመልሳት፡፡
አሁን ባጭር ታጥቀን እንሥራ፡፡ የዘመናት መከራን የቻለ ጫንቃችን ብልፅግናን መሸከም አይሳነውም፡፡
አሁን የድህነትን ድሪቶ አውልቀን የብልፅግናን ፅዱ አልባሳት እንጎናፀፍ፡፡ ድሪቷችን ሲወልቅ ይበርደናል፡፡ ያ ግን ሃላፊ ነው፡፡
አሁን ለፅልመት የለኮስነውን ኩራዝ አጥፍተን በሙላት የፀሐይ ብርሃን እንጓዝ፡፡ በጭለማ ያዘገምን ህዝቦች፤ በብርሃን መራመድ አይሳነንም፡፡
አሁን የድህነትን፣ የማይምነትንና የበታችነትን ሬሳ ታቅፈን አንቀመጥ፡፡ እሱን አልቅሰን እንቅበረው። እርማችንን እናውጣና አዲስ ህይወት እንጀምር፡፡ ስላለፈው የጽልመት ዘመን ማላዘናችንን በዚሁ እናብቃ፡፡
አሁን ፀሐይ ወጥታለች፡፡ ጽልመት ነው ብለን ለዘመናት የከደንነውን ዓይን በድፍረት መግለጥ አለብን፡፡ የድንጋሬ ህመም ይኖራል፡፡ ግን ሃላፊ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኮከብ ለዘላለም ያብራ!! አሜን!

Published in ጥበብ

እርስዎ፤ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የጥሬ ሥጋ ወዳጅና አድናቂ ከሆኑ አካባቢዎቹን በሚገባ ያውቋቸዋል፡፡ ህዝበ አዳም ተሰልፎ ጥሬውን ከጥብሱ የሚያማርጥባቸው ሥፍራዎች ናቸው። ከአዲሱ ገበያ  እስከ ገዳም ሰፈር፣ ከዶሮ ማነቂያ እስከ ልደታ ድረስ አካባቢዎቹ በጥሬ ሥጋ አቅርቦታቸው ይታወቃሉ፡፡ በተለይ፤ በደመወዝ ሰሞንና በሳምንቱ እረፍት ቀናት ቤቶቹ በቁርጥ ሥጋ ተመጋቢዎች በእጅጉ ይጨናነቃሉ፡፡ በእነዚህ ቤቶች እንኳንስ መቀመጫ መቆሚያ ሥፍራ ማግኘት ይቸግራል። ወንበርና ጠረጴዛ በወጉ አግኝቶ ከሚስተናገደው ተመጋቢ ቁጥር ይልቅ በትንንሽ ዱካዎችና የለስላሣ ሣጥኖች ላይ ተቀምጦ፤ ጥሬ ሥጋ የተቆለለበትን ትሪ ጉልበቱ ላይ አስቀምጦ የሚበላው ተመጋቢ ይበልጣል። ቤቶቹ “እስቲ ምሣ እየበላን እንጫወት” ለሚሉ አይነት ሰዎች (ቀጠሮዎች) በፍፁም አይመቹም። እየተጣደፉ ገብተው፣ ባገኙት ነገር ላይ ተቀምጠውና በጥድፊያ ተመግበው፣ በጥድፊያ ከፍለው ለሚወጡት ብቻ ነው የሚሆኑት፡፡
ታዲያ እነዚህን ቤቶች የሚያመሳስላቸው አንድ የጋራ ጉዳይ አላቸው፡፡ ከአዲሱ ገበያ እስከ ጊዮርጊስ፣ ከዶሮ ማነቂያ እስከ ልደታ ቤቶቹ የሚመሳሰሉባቸው ዋነኛው ጉዳይ የመፀዳጃ ቤቶቻቸውና የምግብ ማብሰያ ክፍሎቻቸው የተያያዙ መሆናቸው ነው። እዛው መፀዳጃ ቤቱ በራፍ ላይ ምግብ አብሣይ ሠራተኞች፣ ደንበኛ ያዘዘውን ምግብ ለማድረስ ተፍ ተፍ ሲሉ ይታያሉ። እጅግ የሚሰነፍጥ ሽታ ባለው መፀዳጃ ቤት ለደቂቃዎች የመቆየት ብርታት ካለዎት፣ የስንት ደንበኛ ምግብ ተሰርቶ እንደሚወጣ መቁጠር ይችላሉ፡፡
የዚህኑ መፀዳጃ ቤት ግድግዳ ተደግፈው ያዘዙት ምግብ መድረስ አለመድረሱን በጉጉት የሚጠባበቁ በርካታ የሆቴሉ ደንበኞች አሉ። በእነዚሁ ቤቶች የእጅ መታጠቢያውም የሚገኘው በመፀዳጃውና ማብሰያ ክፍሉ አካባቢ ነው፡፡ ከመፀዳጃ ቤቱ የሚሰማውን ነጐድጓዳዊ ድምፅ በጆሮ፣ የሚተነፍገውን ሽታ በአንፍጫ እየተቀበሉ መፀዳጃ ቤቱ ደጃፍ ላይ ተቀምጦ መመገብ ለበርካታ አዲስ አበቤዎች አዲስ ነገር አይደለም። በእዚህም ሳቢያ በቀላሉ ሊያልፍ ከሚችል ቀላል ህመም እስከሞት ለሚያደርሱ በሽታዎች መጋለጥ ለከተሜው ነዋሪ የተለመደ ነው፡፡
በ2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ፋኩሊቲ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙና የመፀዳጃ ቤት አላቸው ተብለው ከተመዘገቡ አነስተኛ ምግብ ቤቶች ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት የመፀዳጃ ቤቶቻቸውና  የማብሰያ ክፍሎቹ ተጐራባች ናቸው። መፀዳጃ ቤቶቹ በአብዛኛው ንፅህና የጐደላቸውና እጅግ የሚተነፍግ ሽታ ያላቸው ሲሆኑ፤ አንዳንዳቹም ወለላቸው የተበላሸና ለአይን በእጅጉ የሚያስፀይፉ ናቸው። በከተማዋ ከመመገቢያ ሥፍራ የራቁ ንፁህ የመፀዳጃ ቤቶች ያላቸው ምግብ ቤቶችን ማግኘት ይናፍቃል፡፡
ትቀልዳላችሁ? ምግብ ለመመገብ ከተቀመጣችሁበት የመፀዳጃ ቤቱ በራፍ ላይ ወደ መፀዳጃ ቤት የሚገባውን ሰው ለማሳለፍ አስር ጊዜ ብድግ ቁጭ ማለት ሁሉ ግድ ነው፡፡ ግን አማራጭ የለም፤ አብዛኛው የከተማው ነዋሪ ለመመገብ አቅም የሚኖረው በእነዚህ ቤቶች ነው፡፡ ምግቡንና ታይፎይዱን በአንድ ላይ በልቶ ከፍሎ ይወጣል። ታይፎይዱ ደግሞ ቆይቶ ያስከፍለዋል፡፡ ይህን አስተያየት የሰጠኝ በእነዚህ ምግብ ቤቶች ደንበኛ የሆነ ወጣት ነው፡፡  
እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ የሆቴሎችና ምግብ አቅራቢ ድርጅቶችን የጥራትና ንፅህና ደረጃ በመቆጣጠር እርምጃ የመውሰድ ሃላፊነት የተሰጠው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ለሚገኘው “የጤናው ዘርፍ” የተባለ ክፍል ነበር፡፡ ከ1995 ዓ.ም በኋላ ግን ኃላፊነቱ ለከተማው ጤና ቢሮ ተሰጥቶ “ደንብ ማስከበር” በሚባሉ ኃይሎች ቁጥጥርና እርምጃ የመውሰዱ ተግባር እንዲቀጥል ተደረገ፡፡
ሆኖም ግን፤ ምግብ ቤቶቹን በየጊዜው የማየቱና የንፅህና ሁኔታቸውን የመቆጣጠሩ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት፣ በአግባቡና በሥርዓቱ ሊከናወን አልቻለም፡፡ በአጥፊዎቹ ላይም በቂ እርምጃ እየተወሰደ አይመስልም፡፡ በዚህም ሣቢያ ዛሬ አዲስ አበባችን በአብዛኛው መመገቢያና ማብሰያ ክፍሎቻቸው ከመፀዳጃ ቤቶቻቸው ጋር የተጐራበቱ ምግብ ቤቶች መናኸሪያ ለመሆን በቅታለች፡፡
በእነዚህ ምግብ ቤቶች የሚመገቡ ሰዎች እንደ ሺጌላ፣ ሳልሞኔላ፣ ካምፒሎባክተር፣ ኢ-ኮላይ-ሊስቴሪያና ቦቱሊኒየም ለመሳሰሉ በሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች በቀላሉ ሊጋለጡ እንደሚችሉና በእነዚህ ባክቴሪያዎች ሣቢያ የሚመጡ በሽታዎችም እስከ ሞት ሊያደርሱ እንደሚችሉ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በላብራቶሪ ቴክኒሺያንነት ከ10 ዓመት በላይ ያገለገለው ሰለሞን ተካ እንደሚናገረው፤ የአብዛኛዎቹ ምግብ ወለድ በሽታዎች ምንጭ የሆኑት ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶችና ጥገኛ ትላትሎች በንፅህና ጉድለት የሚከሰቱና በተለይም በመፀዳጃ ቤት ሣቢያ ሊመጡ የሚችሉ ናቸው፡፡
የምግብ ማብሰያና የመፀዳጃ ክፍሎቻቸው  በተጐራበቱ ምግብ ቤቶች በመመገብ ሳቢያ ከሚከሰቱ በሽታዎች መካከል የሆድ ጥገኛ ትላትሎች፣ የአንጀት ቁስለትና ሄፒታይተስ ጥቂቶቹ እንደሆኑ የሚናገሩት የጤና ባለሙያዎች፤ በሽታዎቹም ህመምተኛውን ለሞት ሊያደርሱት እንደሚችሉ ይገልፃሉ፡፡
በበሽታው ተይዘው ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡና የላብራቶሪ ምርመራ ከሚታዘዝላቸው ህሙማን መካከል አብዛኛዎቹ የተበከለ ምግብና ውሃ ወለድ የሆኑ የተለያዩ የአንጀትና የሆድ ጥገኛ ትላትሎች በምርመራ እንደሚገኝባቸው የላብራቶሪ ባለሙያው ይናገራል፡፡
የከተማዋን ነዋሪ ጤና እጅግ አሣሣቢ ደረጃ ላይ ያደረሱት እነዚህ ምግብ ቤቶች፤ ፈቃዳቸውን በሚያድሱባቸውና የጤና ቢሮ ተቆጣጣሪዎች ይመጣሉ በሚባሉባቸው ጊዜያት፣ ክፍሎቻቸውን አፅድተውና አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ አሟልተው፣ አንዳንዴ ደግሞ ተቆጣጣሪ እየተባሉ ከሚላኩ ሠራተኞች ጋር በሙስና ተደራድረው ቁጥጥሩን ያልፋሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ነፃ ወጡ ማለት ነው። ቤቶቹን በድጋሚ ዞር ብሎ የሚያይና ንፅህናቸውን የሚከታተል ባለመኖሩ የቀጣዩ አመት ፈቃድ እደሣ ጊዜ እስከሚደርስ ማብሰያ፣ መመገቢያና መፀዳጃ ክፍሎቻቸውን አቀላቅለው ከጤናችን እያጣሉን ይቀጥላሉ፡፡
85 በመቶ ይሆናሉ ተብለው በጥናቱ በተጠቀሱት ሆቴሎችና ምግብ ቤቶች በየዕለቱ የሚመገበው የከተሜ ነዋሪ ቁጥር ቀላል አይደለም። ይሄ ደግሞ ሁኔታውን እጅግ አሣሣቢ ያደርገዋል። ይህንን ችግር ለማስወገድና የህብረተሰቡን አሳሳቢ የጤና ሁኔታ ለመታደግ የሚቻለው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የየድርሻቸውን መወጣት ሲችሉ ቢሆንም፤ ህብረተሰቡም ለራሱ ጤና ማሰብ ይገባዋልና ከእነዚህ አይነት መመገቢያ ሥፍራዎች ራሱን በመቆጠብ፣ የሚመገብበትን አካባቢ መምረጥ ይገባዋል፡፡ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንዲሉ፡፡

Published in ዋናው ጤና
Saturday, 14 December 2013 12:39

ስለ ይቅር ባይነት

አባቴ ሆይ፤ የሚሰሩትን ያውቃሉና ይቅር በላቸው፡፡
ካርል ክራዩስ (የኦስትሪያ ፀሐፊ)
ጠላቶችህን ምንጊዜም ይቅር በላቸው፤ ስማቸውን ግን ፈጽሞ እንዳትረሳ፡፡
ሮበርት ኬኔዲ (አሜሪካዊ ፖለቲከኛ)
እኔ ጠላቶቼን ይቅር ማለት አይጠበቅብኝም፤ ሁሉንም ገድዬ ጨርሻቸዋለሁ፡፡
ራሞ ማርያ ናርቫዝ (ስፔናዊ ጄነራልና ፖለቲከኛ)
ታላቅ ሰው የትላንት ጉዳቶቹን እያሰበ አይብከነከንም፡፡
(ዩሪፒደስ (ግሪካዊ ፀሐፌ ተውኔት)
ለቡጢህ ምላሽ የማይሰጠህን ሰው ተጠንቀቀው! እርሱም ይቅር አይልህ፤ ለራስህ ይቅርታ እንድታደርግም አይፈቅድልህ፡፡
ጆርጅ በርናንድ ሾው (አየርላንዳዊ ፀሐፌ ውኔት)
ሌሎችን ተጠያቂ እንደምታደርግ ራስህን ተጠያቂ አድርግ፤ ለራስህ ይቅርታ እንደምታደርግ ሌሎችንም ይቅር በል፡፡  
የቻይናውያን አባባል
ሰው አንዴ ከተፀፀተ በኋላ ጥፋቱን ፈጽሞ አስታስታውሰው፡፡
የሂብሩ አባባል
የፈለገ ቢሆን ከአምስት ዓመት በላይ ሰው ላይ ቂም አልይዝም፡፡  
ዊሊያም ኬኔዲ (አሜሪካዊ ፊልም ፀሐፊናደራሲ)
እግዚአብሔር ይቅር ይበልሽ፤ እኔ ግን ፈጽሞ ይቅር ልልሽ አልችልም፡፡
ቀዳማዊት ኤልዛቤት (እንግሊዛዊት ንግስት)
እውነትን ውደድ፤ ለስህተት ግን ይቅርታ አድርግ፡፡
ቮልቴር (ፈረንሳዊ ፀሐፊና ፈላስፋ)

Published in የግጥም ጥግ

ኢህአዴግ ይቅር የተባባለው ከአና ጐሜዝ ጋር ብቻ ነው!
የብሄር ብሄረሰቦች ቀን “የፍቅር ቀን” መስሎኝ?

እኔ የምላችሁ … በጅግጅጋ የተከበረው ስምንተኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን እንደጉድ ደምቆ ተከበረም አይደል (ያውም የግመል ወተት በቧንቧ እየተቀዳ!) ለካስ እውነተኛው “እንግዳ ተቀባይነት” ያለው የሶማሊያ ህዝብ ጋ ነው፡፡ ምንም እንኳን በአካል ቦታው ላይ ተገኝቼ በዓሉን ለመታደም ባልታደልም ሁሉንም መረጃ ከኢቴቪና ጅግጅጋ ከሄዱ ባልደረቦቼ አግኝቼአለሁ፡፡ “አጃኢብ ነው መስተንግዶ!” ተብሏል፡፡
በርካታ ከመሃል አገር የሄዱ የበዓሉ ታዳሚዎችም የሶማሊያውያንን ጢም ብሎ የተትረፈረፈ ፍቅርና እንግዳ አክባሪነት እንደጉድ መስክረዋል፡፡ አንዷ ከአዋሳ የሄደች የበዓሉ ታዳሚ ስትናገር፤ “ከርቀቱ አንፃር መንገዱ ሊያደክመን ይገባ ነበር፤ ግን ፍቅራቸው አላደከመንም” ብላለች፡፡ እናላችሁ … ከዚህ ቀደም ከተከበሩት “የብሔር ብሔረሶች ቀን” ሁሉ የዘንድሮው “ሳይታሰብ” ደምቋል፤ ፈክቷል… እያልኳችሁ ነው፡፡ ትንሽ ያልተመቸኝ ግን ምን መሰላችሁ? ለፍቅርና እርስ በርስ ለመተዋወቅ፣ ለመከባበርና ለመቻቻል የታሰበው በዓል፤ ለመወቃቀሻና ለመወነጃጀያ መዋሉ ነው። እኔ የምለው … እንዲህ የሚመስለውን ውይይት በጂግጂጋ ያዘጋጀችው የኢቴቪ ጋዜጠኛ ሙያውን ተወችው እንዴ? (ካድሬ ነዋ የምትመስለው!)
ከምሬ ነው … የድሮ ቁርሾ ማንሳት ፋይዳው ምንድነው? (የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የፍቅር ቀን መስሎኝ?!) እስቲ አስቡት … የደጋ ሰው ሶማሌዎችን “ሽርጣም ሶማሊያ ይል ነበር፤ ሶማሌዎች ደግሞ “ህፃን ልጅ ሲያለቅስ አበሻ እንዳልጠራብህ እያሉ ያስፈራሩ ነበር፡፡” ወዘተ…የሚሉ አሉታዊ አስተያየቶች ምን ይሰራሉ? ደሞ እኮ ሁሉም በደልና ጭቆና የተፈፀመው ዛሬ ሳይሆን በንጉሱና በደርጉ ዘመን ወይም ከዚያ በፊት ነው፡፡ እናላችሁ … ይሄን ቁርሾ መቆስቆስ ትውልዱን ለማፋቀር ነው ወይስ ለማቃቃር? በኢቴቪ አስተያየት የሰጠች አንዲት የበዓሉ ታዳሚ ምን አለች መሰላችሁ? “ትላንት ጥሩ ያልሆነ ነገር ነበር፤ እሱ ትላንት ተሰርቶም ተወርቶም አልፏል!” (ማን ነበር “የምንለውን ብለናል፤ አሁን ወደ ተግባር” ያለው?) ሰው እንዴት የዛሬ ነፃነቱን በትላንት ጭቆና ላይ ያከብራል? (ያውም በቁጭት ተሞልቶ!) እውነታውን ለመሸሽ ብዬ እንዳይመስላችሁ! በቀደሙት መንግስታት ተፈፀሙ የተባሉትን የበደል ታሪኮች ለመካድም አይደለም፡፡ እንዲህ ያሉ የአገራችን የቆዩ በደሎች ግን ትክክለኛ ቦታቸው የታሪክ መፃሕፍት ውስጥ ይመስለኛል፡፡ (የፈለገ እዚያ ያያቸዋል!) እንዴ … አሁን እኮ Live እየቀረበ ነው፡፡ “አውጫጭኝ” ሁሉ ይመስላል!! ችግሩ ግን በዳይና ተበዳይ በሌሉበት ሆነ! እንዴ … ሌላ የተሻለ በጐ ታሪክ የለንም እንዴ? (በ“አዲሲቱ ኢትዮጵያ” አሮጌ ልብ ይዘን አንዘልቅም?)
እኔማ ምን አሰብኩ መሰላችሁ? የብሄር ብሄረሰቦች ቀን “ይቅር የምንባባልበት ቀን” እንዲሆን! በእርግጥ የአሁኑ ትውልድ የፈፀመው በደል የለም። ላለፉት ትውልዶች ነው ይቅር የምንባባለው፡፡ (“የአባት ኃጢያት ለልጅ ይተርፋል” አሉ!) እናም ይቅር ብለንና ተባብለን ስናበቃ … በፍቅር የተሟሸች አዲሲቱን ኢትዮጵያ ወደ መገንባቱ ብንገባ ሸጋ ይመስለኛል፡፡ (የሚሰማኝ ሲኖር አይደል!)
በብሄር ብሄረሰቦች ቀን ያለፈውን በደልና ጭቆና ማራገብ ለመረጠው አውራው ፓርቲ የማሳስበው ጉዳይ አለኝ፡፡ ምን መሰላችሁ? የብሄር ብሄረሰቦች መብት ተከብሯል በሚባልበት በአሁኑ ወቅት በየክልሉ “ማንነታችን ተጨፈለቀ”፤ “በቋንቋችን የመጠቀም መብታችንን ተነጠቅን” የሚሉ የተለያዩ ብሄሮች አሉና ብልሃትና ጥበብ የተመላበት መፍትሔ መስጠት ይገባል፡፡ (የትላንቱን ስንተርክ፣ ዛሬያችን ትላንት እንዳይሆን እኮ ነው!)
እውነቴን ነው የምላችሁ…ቢያንስ ለልጆቻችን የቁርሾ ታሪክ እንዳናስረክብ መጠንቀቅ ይገባናል። ያለዚያ ግን አዲሱ ትውልድ ይታዘበናል (እኛ የ60ዎቹን ትውልድ እንደታዘብነው!) እኔ የምለው ግን … መቼ ነው የጦቢያ የ60ዎቹ ፖለቲከኞች ይቅር ተባብለው የሚተቃቀፉት? (እርስ በእርሳቸው የተፋጁት ለጦቢያ መስሎኝ!) እንዴ … የተኮራረፈ ትውልድ በዛ እኮ!  ከምሬ ነው … እዚህ ጉዳይ ላይ “ቸክለን” ካልሰራን ለመጪው ትውልድ የሚያኮራ ታሪክ አናስረክብም፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን እንደ መንገዱ ልማት፣ እንደ ህዳሴው ግድብ ግንባታ፣ እንደ ባቡሩ ዝርጋታ … ለእርቅና ለአገራዊ መግባባት መትጋት አለበት፡፡ (ያማረ ታሪክ ትቶ ማለፍ ከፈለገ!) እሱ ራሱ እኮ በ20 ምናምን ዓመት የስልጣን ታሪኩ ይቅር የተባባለው ከአና ጐሜዝ ጋር ብቻ ነው (የምር ከሆነ ማለቴ ነው!)
የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ህልፈት ዓለምን “የቀወጠው” እኮ … ያሰሯቸውን ሰዎች ይቅር ብለው መቻቻልና አገራዊ መግባባት ስለፈጠሩ ነው -በፍቅር!! እርግጥ ነው ቀንደኛ ኮሙኒስት ለነበረው አውራው ፓርቲያችን (ያውም የአልባኒያ) ፍቅር … እርቅ… አገራዊ መግባባት … ወዘተ… ላይጥሙት ይችላሉ፡፡ (ትግል ነዋ የለመድነው!) ድህነትን ለማጥፋት ትግል! አገሪቱን ለማበልፀግ ትግል! የሃይማኖት መቻቻል ለማምጣት ትግል! ምሩቃን ወደ ኮብል ስቶን ስራ እንዲገቡ ትግል! … (ከ“ትግል” ወደ “ፍቅር” መግባት እኮ ፈታኝ ነው!)
እኔ የምላችሁ … በማንዴላ ህልፈት (ያውም በ95 ዓመታቸው አርፈው!) ማን ያላዘነ፣ ማን ባንዲራውን ዝቅ አድርጐ ያላውለበለበ፣ ማን ለቀብር ደቡብ አፍሪካ ያልገባ አለ? ቀብር ሳይሆን የዓለም መሪዎች ስብሰባ እኮ ነው የመሰለው! (የሊቢያው ጋዳፊም እኩል ሞቱ ይባላል?) “አሟሟቴን አሳምረው” የሚባለው ለካ ያለ ነገር አይደለም፡፡ (“የስልጣን አወራረዴን እንዳወጣጤ አሳምረው” ቢባልም ያስኬዳል!) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ በማንዴላ የቀብር ሥነስርዓት ላይ ንግግር ሲያደርጉ፤ “ከአሁን በኋላ የማንዴላ ዓይነት ሰው አይፈጠርም” በማለት ዓለምን ሁላ ተስፋ አስቆርጠዋል፡፡ (ግን እኮ እውነት ነው!) የማንዴላ ህልፈት በተሰማ በነጋታው፣ የጦቢያም መንግስት የሀዘን መግለጫ  በኢቴቪ አስተላልፎ ነበር፡፡ ከሁሉም የማረከኝና ያስደመመኝ ግን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ያወጣው የሃዘን መግለጫ ነበር፡፡ በተዋበ ቋንቋ አምሮና ተከሽኖ የተጠናቀረው የጽ/ቤቱ የሃዘን መልዕክት፤ የደቡብ አፍሪካን ህዝብ “አይዞአችሁ! የታላቅ መሪ ሞት እንዴት መሪር እንደሆነም እኛም ቀምሰነዋል” በማለት እንዲፅናኑ ምኞቱን የሚገልፅ ሲሆን ኢህአዴግና የማንዴላ ፓርቲ ANC ያላቸውን የዓላማ አንድነትም በቀጥታ ሳይሆን በዘወርዋራ ለመጠቆም ይሞክራል፡፡ ኢህአዴግን ከ“አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ”፣ የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር ከማንዴላ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካው አቻ ጋር ለማስቀመጥ ፅ/ቤቱ እንዴት እንደለፋ መግለጫው በደንብ ይጠቁማል፡፡ ግን ንፅፅሩ ወይም ምስስሉ ለምን አስፈለገ? (ኩሩ ህዝብ እኮ ነን!)  በነገራችሁ ላይ … የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤትና የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሳይቀላቀሉ አልቀረም። (የሀዘን  መግለጫው ኢህአዴግ ኢህአዴግ ሲሸተኝስ!) ግን እኮ … ኢህአዴግና መንግስት አብረው ቢያዝኑና ለቅሶ ቢደርሱ ኃጢያት የለውም (ኧረ ፅድቅ ነው!) ኢህአዴግና የማንዴላው ፓርቲ ANC በነፃነት ታጋይነታቸው ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ከቂም በቀል ይልቅ እርቅ፣ ይቅር መባባልና መቻቻልን መፍጠር … በሚለው ረገድ ግን ሆድና ጀርባ ናቸው፡፡ “የለም… አንድ ናቸው” ብሎ የሚሟገት ካለ፣ ኢህአዴግ ላይ ፈተና ሊያበዛበት የፈለገ ሰው ነው ማለት ነው፡፡ (ኢህአዴግ ከፍቅር ይልቅ ትግል ብሏላ!) ከሁሉም የሚገርመው ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግም ተቃዋሚዎችም ማንዴላን አድናቂና አወዳሽ መሆናቸው ነው፡፡ ከማንዴላ የመቻቻል፣ የመግባባትና እርቅ የመፍጠር ተምሳሌታዊ መርሆዎች ግን አንዱንም አይተገብሩም፡፡ (መሆን ሌላ፤ መመኘት ሌላ!)  

ባለፈው ሳምንት በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “በመዲናዋ ምስጢራዊ የወሲብ ገበያ ደርቷል” በሚል ርእስ በመታሰቢያ ካሳዬ የተጻፈውና በህብረተሰብ አምድ ላይ የተስተናገደው ጽሁፍ፣ ከሰሞኑ ከመጻሕፍት አዟሪዎች ደረት ላይ የማይጠፋውንና በማህበራዊ ድረ ገጾች ትኩስ መነጋገሪያ የሆነውን “ሮዛ” የተሰኘ መጽሀፍ አስታወሰኝ። ሁለቱም ጸሀፍት ለአብዛኞቻችን አዲስ አበቤዎች እንግዳ የሆኑና የማናውቃቸውን የመዲናችንን አስገራሚ ድብቅ እውነታዎች አስቃኝተውናል፡፡ የዛሬ ጽሁፌ አቢይ ትኩረት ግን “ሮዛ” በሚል ርእስ ለህትመት የበቃውን የሮዛ ይድነቃቸው የእለት ማስታወሻዎች ስብስብ መጽሀፍ ላይ ሂሳዊ ምልከታን ማቅረብ ነው፡፡
የእለት ማስታወሻዎች ተሰብስበው በመጽሀፍ መቅረባቸው በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ውስጥ የተለመደ አይደለም፤ በቅርብ አመታት ውስጥ ለህትመት የበቁ የስመ-ጥር ኢትዮጵያውያን ግለ-ታሪክ መጻህፍት ከእለት ማስታወሻዎች ስለመጠናቀራቸው እስካሁን ያገኘሁት ተጨባጭ ፍንጭ የለም፡፡

ጎምቱው ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ማንኛውንም የተለየ ቅጽበት ባስተዋለ ቁጥር ማስታወሻ ደብተሩን ከኪሱ አውጥቶ የመሰጠውን ቅጽበት፣ ሃሳብ ወይም ክስተት በዝርዝር የመጻፍ ቋሚ ልምድ እንደነበረው የቀድሞ የስራ ባልደረቦቹና ወዳጆቹ በአንድ አጋጣሚ አጫውተውኛል፡፡ ከነስህተትና ድብቅ አጀንዳቸውም ቢሆን ከነዚህ ማስታወሻዎች ተነስቶ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”፣”የደራሲው ማስታወሻ” እና “የስደተኛው ማስታወሻ” የተሰኙትን መጻህፍት ለህትመት እንዳበቃ ራሱ በስደተኛው ማስታወሻ ላይ ይገልጻል፡፡ ዛሬ ለዳሰሳ የመረጥኩት “ሮዛ” የሚል ስያሜ የተሰጠው መፅሐፍም ሮዛ በምትባል ኢትዮጵያዊት ኮማሪት የተጻፈ የግል ማስታወሻ ነው፡፡ ምንም እንኳ የግል ማስታወሻዎቿ አርታኢ እጅ ላይ ወድቀው መጠነኛ የይዘትና የቅርጽ ለውጦች ቢደረጉባቸውም የግል ማስታወሻዎችን ወደ መፅሐፍ ቀይሮ በማሳተም ረገድ ምናልባትም ቀዳሚ ስራ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡
ከዚህ የስነ ጽሁፍ ዘውግ ጋ ለመጀመሪያ ጊዜ በውል የተዋወቅነው አዶኒስ ከአመታት በፊት ወደ አማርኛ ተርጉሞ ባቀረበልን “The Diary of Ana Frank” (የአና ፍራንክ ማስታወሻ) በሚለው መጽሀፍ ይመስለኛል፡፡ አና እነዚህን በመላው አለም በበርካታ ቋንቋዎች ተተርጉመው በሚሊዮኖች ኮፒ የተሸጡላትን የእለት ማስታወሻዎች የከተበችው በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በሆላንድ ርእሰ መዲና አምስተርዳም ከናዚዎች በተደበቀችባት ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ በድርሰት ስራቸው የተደመምንባቸው በርካታ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ደራሲያን ስራዎች ከደራሲያኑ የእለት ማስታወሻዎች የተወለዱ ነበሩ፡፡ ለአስረጅነት የቨርጂንያ ዉልፍን፣ አዳም ረታ በ”እቴ ሜቴ ሎሚ ሽታ” ድርሰቱ ውስጥ የሚያነሳትን ዝነኛዋ የኢሮቲክ ልቦለዶች ደራሲ የሆነችውን አናይስ ኒንን፣ ለየት ባሉት አጫጭር ልቦለዶቹ የሚታወቀውን ፍራንዝ ካፍካን፣ የዝነኞቹን አሜሪካዊያን የኢሮቲክና ሮማንቲክ ልቦለድ ደራሲዎቹን የኤሪካ ዮንግንና የሳንድራ ብራውንን ስራዎች ማንሳት እንችላለን፡፡
አናይስ ኒን “የኔም ሆነ የሌሎች እውነተኛ ማንነት በአንዳች አይነት የስሜት ጡዘት ወይም ቀውስ ውስጥ ስለሆነ እነዚህ ቅጽበቶች በምንም ሁኔታ እንዲያመልጡኝ አልፈቅድም፤ በፍጥነት አንዳች ሳላስቀር በእለት ማስታወሻዎቼ ላይ አሰፍራቸዋለሁ” ብላ ነበር፡፡ ፍራንዝ ካፍካ  “በህይወታችን የተለያዩ ምእራፎች ያሳለፍናቸውን የደስታና የሀዘን፣የጭንቀትና የፈንጠዝያ፣የድሎትና የውጣ-ውረድ ጊዜያት በእለት ማስታወሻዎቻችን በኩል መለስ ብለን ስንመለከታቸው በርግጥም መኖራችንን፣ ከመኖርም አልፈን የኖርነውን በጽሁፍ ለዘለቄታው ማስቀመጣችንን በውል እንገነዘባለን፤ ከእለት ማስታወሻችን በተሻለ የኖርነውን ህይወት፣ ቅጽበታዊ ስሜቶቻችንን ሳይቀር በግልጽነትና በታማኝነት የሚዘግብልን ድርሳን የለም” ይላል፡፡ ስመ - ጥሩ ደራሲ ዴቪድ ሴዳሪስ በበኩሉ “የእለት ማስታወሻዎቻችን ቢያንስ በሁለት  ምክንያቶች ይጠቅሙናል፤ ባለፈ ብስጭታችን፣ ስቃያችን፣ ስህተታችን፣ ድክመታችን፣ እንጭጭነታችንና ውጣ ውረዳችን ዘና እያልን እንዳንደግማቸው ትምህርት እንወስዳለን፤ ‘መጋቢት 3 ቀን 1998 ላይ እኮ እንዲህ ብለህ ነበር’ ብለን ክርክር በመጀመር ሙግት እንረታበታለን” ሲል ተናግሯል፡፡
ሮዛ ራሷም ለዳሰሳ በመረጥኩት ማስታወሻዋ ውስጥ እንደምትገልጸው ኮሌጅ የበጠሰች ሴተኛ አዳሪ ናት። ለሮዛ ዳዬሪዋ (የእለት ማስታወሻዋ) ብቸኛ የሚስጥር ጓደኛዋ የሆናት ይመስላል፤ ይህን የግል ማስታወሻዋን ነው እንግዲህ አደባባይ ያሰጣችው፡፡ በዚህች ምድር ላይ ገሚስ አድሜን ያሳለፈች የአገር ልጅ ለነገ ሳትል ጥብቅ ሚስጢሯን ሁሉ በመጸሐፍ መልክ ድንገት ስትዘከዝክ “ለምን?” ማለታችን አይቀርም፡፡ እኔም ለምን ብዬ ደጋግሜ ጠየቅኩ፡፡ መላምት እንጂ መልስ አላገኘሁም፡፡ ምናልባት ከብዙዎቹ ሴተኛ አዳሪዎች በተለየ ኮሌጅ መበጠሷ ህይወቷን ለሌሎች በማሳየት ማህበረሰባዊ ግዴታዋን ለመወጣት አስባ ይሆን?ምናልባት ሲሶ እድሜዋን የኖረችበትንና እሷ እምብዛም የማትቆጭበትን የቡና ቤት ህይወት በመተረክ ርካሽ ዝናን በአቋራጭ ለማግኘት አቅዳስ ይሆን? ነው ወይንስ ሙአመር ጋዳፊን ማግኘቷን እንደ ታላቅ ስኬት በመቁጠር እዩልኝ ስሙልኝ እያለችን ይሆን? እነዚህን ሁሉ መላምቶች ለመሰንዘር የተገደድኩት መጽሀፏ ውስጥ ምንም አይነት አስረጅ ባለማግኘቴ ነው፡፡ በመጸሐፉ የመጀመርያዎቹ ጥቂት ገጾች መረዳት የቻልኩት ሮዛ  ከያንዳንዱ የ ‹‹ሾርት›› እና የ‹‹አዳር›› ቢዝነስ በኃላ የዕለት ማስታወሻ የመያዝ ልምድ እንዳላት ብቻ ነው፡፡ ምናልባት መጸሐፉ የራሱ መግቢያ ተበጅቶለት ቢሆን ኖሮ እኛም ከመላምት በዳንንና ስለ ጸሐፊዋ ግብና ተልእኮ ብዙ መረዳት በቻልን ነበር እላለሁ፡፡ “ከሾፌር፣ ከሴተኛ አዳሪ፣ ከዘበኛና ከቤት ሰራተኛ የምታመልጥ አንዳችም የአለም ሚስጥር የለችም” በሚል መሪ ቃል ሽፋኑን ያደመቀው ይህ መጸሐፍ፤ ደራሲዋ የሙአመር ጋዳፊ ድንኳን ውስጥ የዘለቀች ‹‹ጀግና›› መሆኗን ገልጾ የልብ ምታችንን ያፈጥንብናል፡፡
በእርግጥ ይህ መጽሀፍ እስካሁን ካነበብኳቸውና ተመሳሳይ ይዘት ካላቸው መጻህፍት በብዙ መልኩ እንደተለየብኝ አልክድም፡፡ መጽሀፉ በርካታ አመታትን በዲፕሎማቶችና ከፍ ባለው ማህበረሰብ ዙርያ በሴተኛ አዳሪነት ህይወት ውስጥ ባሳለፈች፣ ከአንድም ሁለት ሶስት ዓለምአቀፍ ቋንቋ በምትናገር የተማረችና፣ ሯሷን በንባብ የገራች ኮማሪት መጻፉ ብቻ አይደለም ልዩ የሚያደርገው። አጻጻፏ በራሱ አንባቢ ላይ በግድ ቅጽበታዊ ስሜትን የማጋባት ባህሪ አለው፡፡ ስታዝን ይከፋናል፣ስትደሰት እንስቃለን፣ስትበግን እንንገበገባለን፣ ስትስቅ ፈገግ እንላለን…በማያገባን እያስገባችን ስሜታችንን ትሾፍረዋለች፡፡ እለታዊ ማስታወሻዋ የእንቶ ፈንቶ ጉዳይ ቢመስልም የዘመናችንን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ፣፣ባህላዊ፣ሃይማኖታዊና ስነልቦናዊ እውነታዎች በማስታወሻዎቿ በኩል በግርድፉ ታሳየናለች። ይህንን ደግሞ ከአንዲት ኮማሪት የምንጠብቀው ስላይደለ እንገረማለን፡፡ የቡና ቤት ሴት ሆናም የኛን የሞራልና መንፈሳዊ ዝቅጠታችንን ጥልቀት ስትነግረን እንድንሸማቀቅ አድርጋ ነው፡፡ በዕለት ማስታወሻዋ የመኝታ ገድሎቿን እየተረከችልን እሷን ሳይሆን እኛን እንድንታዘብ የሚያደርግ ስሜትን ትረጭብናለች፡፡ ይህንን ማድረግ የቻለችው ከልቧ በፍጹም የተቆርቋሪነት ስሜት ስለምትጽፍ ይሆናል፡፡ ከኪነ-ጥበብ ስራ በላይ ዘመንን ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳይ ነገር ያለ አይመስለኝም ነበር፤ የፈጠራ ስራ ባልሆኑት የሮዛ የግል ማስታወሻዎች ውስጥ ይህንን ሁለንተናዊ የዘመን መንፈስ መመልከቴ ሳያስገርመኝ አልቀረም፡፡
“ሮዛ” እንደ “መሀልዬ መሀልይ ዘ ምናምን” እያሉ ከተድባበ ጥላሁን ቱባ ስራ በኋላ የልብ ካውያ እንደሆኑብን ገበያ ተኮር መጻህፍት የገድለ ወሲብ ጥርቅም አይደለም፤ ወይም ደግሞ ከጋዜጣ ወደ መጽሐፍ እንደተገለበጡት ስራዎች የቡና ቤት ሴቶችን ግልብ ቃለመጠይቅ ወደ ጽሁፍ ቀይሮ ለንባብ ያበቃም አይደለም፡፡ በእርግጥ እነዚህ መጻህፍትም ቢሆን ይብዛም ይነስ በተለያየ ዘመን እና ቦታ የተኖረን ህይወት ለዘለቄታው ለመጪዎቹ ትውልዶች የሚያስተላልፉ ቋሚ ሰነዶች እንደመሆናቸው ሚናቸውንና ጠቀሜታቸውን እያሳነስኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። የስብሀት ገብረ እግዚአብሄር “ሌቱም አይነጋልኝ” መጽሀፍ ባይኖር በንጉሱ ዘመን በውቤ በረሀ የተኖረውን ህይወትና የዘመን መንፈስ እንዴት ማወቅ ይቻለን ነበር?የአለማየሁ ገላጋይ “አጥቢያ” ልቦለድ ባይኖር አሁን ሙሉ በሙሉ በፈረሰችው አራት ኪሎ ውስጥ የተኖረውን ህይወት፣የነበረውን ማህበራዊ መስተጋብር መጪዎቹ ትውልዶች እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? በማህበረሰብ ጥናት ዘርፍ የተሰማሩ ምሁራንስ ከተጻፉ መዛግብት በላይ ምን አይነት ተጨባጭ መነሻ ይኖራቸዋል?
ከላይ ከተጠቀሱት መጻህፍት በተለየ የሮዛ ህይወት በአንድ ሰፈር የተገደበ አይደለም፤የስራዋ ባህሪ ሆኖ መላው አዲስ አበባን ያካልላል፡፡ የሮዛ ህይወት ከድብቅ (ህቡእ)የመዲናችን የአስረሽ ምቺው ቪላዎች እስከ ሼራተን ቪላ እና የሊቢያው መሪ የጋዳፊ ድንኳን ድረስ ይዘልቃል፡፡ ጋዳፊ የአፍሪካ ህብረት አመታዊ ስብሰባን አስታከው የሀበሻ ቆነጃጅትን ለገዙት ‹‹ኤር አፍሪክ›› አየር መንገድ በሆስቴስነት ሲመለምሉ ሮዛ እንዳገኘቻቸው ትገልጻለች፡፡ ከሳቸው ጋርም ባረፉበት ሼራተን ቪላና በድንኳናቸው ውስጥአጭር ሆኖም አስገራሚ ቆይታ ማድረጓንም ትተርክልናለች፡፡ ሮዛ በመጸሕፏ እንደነገረችን ከሆነ ጋዳፊ በርግጥም ወፈፌ ነበሩ። ይህን ቆይታዋን “ከጋዳፊ ጋር ድንኳን መጋፈፍ” በሚለው የመጽሀፉ ሰፊ ምእራፍ ውስጥ በዝርዝር ገልጻዋለች፡፡ ከአመታት በፊት እዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ጋዳፊ በሼራተን ስላካሄዱት የሆስቴስ ምልመላ አጠቃላይ ሂደት በስፋት ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ምናልባት ሮዛ በዚሁ ምልመላ ወቅት አንዷ ታዳሚ መሆኗን መገመት ይቻላል፡፡
በ”ሮዛ”ውስጥ 29 በቀላሉ ከአእምሮ የማይጠፉ ታሪኮች አሉ፡፡ እንደገመትኩት አርታኢው በታሪኮቹ መረጣ ላይ ዋናውን ሚና ሳይወጣ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ለአመታት ከጻፈቻቸው በርካታ የእለት ማስታወሻዎች ውስጥ በሰው ዘንድ ልዩ ስሜት የሚፈጥሩትን ታሪኮች ለማወቅ ሙያዊ ትኩረትና ክህሎት ይፈልጋል፡፡
በ”ሮዛ” ውስጥ በመጀመሪያ ላይ የምናገኘው ታሪክ “ኮሌጅ በጠስን” የሚለውን ነው፡፡ ሮዛ በዚህ ታሪክ ውስጥ የትምህርት ፖሊሲያችን የደረሰበትን ዝቅጠት፣ የራሷንና የኮሌጅ ጓደኞቿን ህይወት በማውሳት ታሳያለች፤
…ኮሌጅ የበጠሱ የኔ “ባቾች” እንዳሁን ዘመን ተመራቂዎች ሁሉም ኮብልስቶን አንጣፊ አልሆኑም፡፡ በባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ አልጋ አንጣፊ የሆኑም አሉ፡፡ እንደኔ እና እንደወይንሸት የተማረ ሸሌ ሆነው የቀሩም አሉ፡፡ እንደ መዲና፣እንደ ራሄል፣እንደ ሂዊ፣እንደ ፎዚያ፣ እንደ ጠይባ አረብ አገር ለግርድና የሄዱም አሉ፡፡ እንደ አብዱልሰመድ(ወሎዬው) በአካውንቲንግ ተመርቀው የመን አገር ፍየል ለማገድ የተሰደዱም አሉ፡፡እንደ ምስኪኑ ሀብትሽ ሰፈር ውስጥ ጸጉር አስተካካይ የሆኑም አሉ፡፡ ሀብትሽ “ አታካብዱ ያው ነው፣ድሮም በጭንቅላቴ ነበር የምሸመድደው አሁንም ጭንቅላት ነው የምከረክመው፤አሁንም ድሮም ከአንገት በላይ ስፔሻሊስት ነኝ!” እያለ ራሱ ላይ ይቀልዳል፡፡ የክላስ ልጆችን ሳስብ እንደ ሀብትሽ አንጀቴን የሚበላኝ ሰው የለም፡፡ ሀብትሽ ለአራት አመት “ስፔስ” እየተመላለሰ፣አይኑ እየተጨናበሰ፣እንቅልፍ እንዳያሸንፈው እግሩን በሳፋ እየዘፈዘፈ፣ ሌት-ተቀን ትምህርቱን ሲሸመድድ ቢኖርም ያቺ ቆሽማዳ ህይወቱ ፈቀቅ አላለችም…(ገጽ-5)
በመጽሀፉ ውስጥ “ዋለልኝ” በሚለው ታሪክ ውስጥ አቸኖ የተባለውን የቺቺንያ ለማኝ እናገኛለን፤ዋለልኝ እንግሊዝ ለንደን ውስጥ በሚገኝ አንድ ግዙፍ ኩባንያ ውስጥ በስራ አስኪያጅነት የሚሰራና በርካታ ሺህ ፓውንድ ደሞዝ የሚከፈለው የቀድሞ የኢህአፓ አባል ነው፡፡ በኢህአፓ ትግል ወቅት በደረሰበት ስነ ልቦናዊ ችግር ምክንያት ወሲብ መፈጸም አይችልም፡፡ የሴት ገላ አቅፎ ለመተኛትም የቻለው በእንግሊዝ ቆይታው ረጅም ጊዜ በወሰደ የስነ ልቦና ህክምና ነው፡፡ በዚህ ቅንጭብ ታሪክ ውስጥ ሮዛ ተራ የህይወት ትዝብቷን እንዴት ከዘመናችን ማህበረ ፖለቲካ ጉዳዮች ጋር አቆራኝታ እንደምትመለከታቸው እንረዳለን፡፡ የሮዛ አንዳንድ ትዝብቶች አጥንታችን ድረስ ዘልቀው የሚሰሙን ናቸው፡፡ ለማሳያ ያህል የአቸኖን ቅንጭብ ታሪክ እንመልከት፡-
ሰኒና ወገቧን ያቀፋት ወጣት ኮንትራት ታክሲ ውስጥ ሊገቡ ሲሉ የእግር አልባው ለማኝ የአቸኖ ድምፅ ገታቸው። ከኋላቸው ስለነበርኩ ለማኙ ምን እንደሚላቸው እየተከታተልኩ ነበር፡፡ አቸኖ ሁሌም እንደሚያደርገው የሌሊቱን ብርድ ለመቋቋም በርካታ አረቄዎችን እንደተጋተ የድምጹ ቅላጼ ያሳብቃል፡፡
“አባቱ!እስቲ ብር ልቀቂብኝ!”
ወጣቱ ምንም ምጽዋት ሳይሰጠው ሰኒን እንዳቀፈ ወደ ታክሲው አመራ፡፡ አቸኖ ከመቅጽበት እሳት ለበሰ፤ሁልጊዜ ነው እንዲህ የሚሆነው፡፡ ሰው ሳይመጸውተው እንዳላየው ሆኖ ለማለፍ ሲሞክር ክፉ ይናገራል፤አቸኖ ሰኒን ያቀፈውን ወጣት ምን ሊለው እንደሚችል እየጠበቅኩ ነበር፡፡
“ትሰማኛለህ ወንድሜ!አንተ እንደዚህ በሰላም አየር የሴት ወገብ እንድታቅፍ እኮ ነው እኔ ባድመ ላይ በሻእቢያ ፈንጂ ሁለት እግሮቼን ያጣሁት! ተጸይፈኸኝ ነው ዞረህ እንኳን ልታየኝ ያልፈለግከው?”አለው፡፡
አቸኖ ምጽዋት ሲጠይቅ ለመላው ቺቺንያ በሚሰማ አስገምጋሚ ድምጽ እያንባረቀ ስለሆነ ያስፈራል…(ገጽ 111-112)
ሮዛ “የተከበሩ ማዳም ኤልዛቤጥ” በሚለው ታሪክ ውስጥ የማዳም ኤልዛቤጥ ግዙፍ የመስቀል ፍላወር ቪላ የሚሰጠውን ህቡእ የወሲብ አገልግሎትና በዚያም የሚደርሰውን አሰቃቂ አጋጣሚ በዕለት ማስታወሻዋ ታስቃኘናለች፡፡ ማዳም ኤልዛቤጥ የእድሜያቸውን ሲሶ በፈረንሳይ ያሳለፉ እመቤት ናቸው፡፡ ከዚህ ታሪክ በርግጥም በመዲናችን ውስጥ በርካታ የማናውቃቸው ገመናዎች መኖራቸውን እንረዳለን። ”ፍቅርተን ማን ገደላት?ባሏ” በሚለው አሳዛኝ ታሪክ ውስጥ ሮዛ የአፍ ወለምታ ህይወትን የሚያክል ውድ ነገር የሚያስቀስፍበትን ገጠመኝ ትነግረናለች፡፡
“ጥኡም ወዲ አስመራ” በሚለው ማስታወሻዋ ውስጥ አባትና ልጅ በአንድ ምሽት ሳያስቡት ከሷ ጋር ለመተኛት በሚያደርጉት ትግል ድንገት ግንባር ለግንባር መገጣጠማቸውን በመተረክ፣ የዘመናችንን እውነታ ፍንትው አድርጋ ታሳየናለች፡፡ ይህንን ታሪክ አንብቦ አለመደንገጥ ይከብዳል፡፡ “የቤዛ አልፋና ኦሜጋ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ደግሞ ወንድም ከቡና ቤት ሴት ጋር እየቀበጠ ከበርካታ አመታት በፊት ከቤት ወጥታ የቀረች እህቱን፣ በዚያው ሆቴል ውስጥ በሴተኛ አዳሪነት ስትሰራ እንደሚያገኛት እንመለከታልን፡፡
የሮዛ የስራ ጸባይ በራሱ በየእለቱ ከተለያዩ የህይወት ጽንፍ የሚመጡ በርካታ ሰዎችን እንደሚያገናኛት ከመጽሀፉ እንረዳለን፡፡ በማስታወሻዎቿ ውስጥ ሮዛ ስለራሷ ገመና ብቻ አይደለም የምትተርክልን፡፡ ስለ ቡና ቤት ሴት ጓደኞቿ(የስራ ባልደረቦቿ)፣አብረዋት ስለተማሩ ወንዶችና ሴቶች፣ ስለፓይለትና ፕሮፌሰር ደምበኞቿ፣ በስካር ነብዘው በተንቋረረ ድምጻቸው “ከኛ በላይ ላሳር” ስለሚሉ ትምክህተኛ ምሁራን፣ስለአፍሪካ ዲፕሎማቶችና ሴሰኝነታቸው፣ራሳቸውን ከፓሪሱ “ኤፍል ታወር” በላይ ቆልለው ስለሚያዩ ዳያስፖራዎች…እያሳቀችን ትተርክልናለች። ደግሞ ማሳቅ ትችላለች፡፡ የስነ-ጽሁፍ አንዱ ግብ አንባቢን ማዝናናት መሆኑ ይታወቃል፡፡
”Usman The Pimp” በሚለው ታሪክ ውስጥ ብዙ አለም-አቀፍ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ የሚናገረውን መልከ-መልካሙን አስጎበኚ ኡስማን እናገኛለን። ኡስማን በቅልጥፍናው በርካታ ሀበሻ ቆነጃጅትን ከአረቦች፣ከነጮች፣ከአፍሪካውያንና፣ከእስያውያን ቱሪስቶች ጋ ያገናኛል፤ሁሌም ባተሌና እረፍት አልባ ነው። የውጭ ዜጎቹን ከሀበሻ ቆነጃጅቱ ጋ የሚያገኛኝበት ህቡእ መረብ ስፋትና ጥልቀት በተለይ በአለም-አቀፍ ስብሰባዎች ወቅት አስገራሚ ነው፡፡ እኛ የዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ እያልን የምናንቆለጳጵሳት መዲናችን፣ በእያንዳንዱ አለማቀፍ ስብሰባዎች ምሽት ታላቅ የወሲብ ንግድ እንደሚካሄድ የምንረዳው በዚሁ የኡስማን ዘ ፒምፕ ታሪክ ውስጥ ነው፡፡ የሴት ደላላ ሆኖ የተነገረን የኡስማን ታሪክ “ተወልጄ እድሜዬን ሁሉ በኖርኩባት አዲስ አበባ እንዴት ይሄ ሁሉ ጉድ መኖሩን እስካሁን አላወቅኩም?” ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡ ሮዛ ከጋዳፊ የፕሮቶኮል ሀላፊ እና ከራሳቸው ከሊቢያው መሪ ጋር እንድትገናኝ አስፈላጊውን ሁኔታ ያመቻቸውም ይኸው ሴት አቅራቢ ኡስማን ዘ ፒምፕ ነው፡፡ ሮዛ ኢትዮጵያዊያን ሴት እህቶቻችን አረብ አገር ብቻ ሳይሆን እዚሁ በአገራችን ለወሲብ ገበያ በስፋት እንደሚቀርቡ ትነግረናለች፡፡ ሴቶቻችንን ለአረቦች በረብጣ ሪያል በመሸጥ ሀብት ንብረት ያፈሩ ሰዎችን ለማሳየትም ይህንኑ ዝናው በከተማዋ ቆነጃጅት ዘንድ የናኘውን ኡስማን ዘ ፒምፕን ታሪክ ታቀርብልናለች፡፡
“ራቁት ጭፈራ ቤቱ ተዘጋ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ሮዛ ደምበል ህንጻ ስር ስለነበረው ’ኢን ኤንድ አውት’ ስለተባለውና ከበርካታ ዓመታት በፊት በፖሊስ አሰሳ ስለተዘጋው ራቁት ቤት ቆይታዋ ታወጋናለች፡፡ ይህ የራቁት ቤት በአሰሳ መልክ ሲዘጋ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በበርካታ የአገራችን ሚዲያዎች በስፋት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ጥቂት ስመጥር ምሁራንና አርቲስቶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ይታወሳል። ሮዛ የቤቱ ታዳሚዎች እነማን እንደነበሩ ብቻ ሳይሆን በዚሁ ህንጻ ውስጥ በሚገኝ ሊፍት ውስጥ ብዙ የወሲብ ገድሎች ይፈጸሙ እንደነበረ በምልሰት ትተርካለች፡፡ እንደምሳሌም ‹‹የሊፍት ቴክኒሻኑ ፈሌ›› በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር ይሆናል ብለን የማናስበውን ድብቅ የሊፍት ውስጥ የቤርጎ አገልግሎት እናገኛለን፡፡
ከታሪክ ታሪክ የሮዛን ስሜት እየተጋራሁ ነው መጽሀፉን የጨረስኩት፡፡ ማስታወሻዎቹ በቀልድና በጨዋታ የተዋዙ ስለሆኑ አዝናንተውኛል፡፡ በየታሪኮቹ ጣልቃ በማህበረሰባችን ሁኔታ ያዘንኩባቸውና የደነገጥኩባቸው ቅጽበቶችም ነበሩ፡፡ 29ኙም ታሪኮች ስሜት ይነካሉ ማለት ይቻላል፡፡ የማስታወሻዎቹ ስነ-ጽሁፋዊ ውበትም ማለፊያ ነው፡፡የሮዛ ለየት ያሉ የህይወት ትዝብቶች፣ ምልከታዎችና ለማንኛውም ነገር ያላት በሳል አስተሳሰብ ይማርካል። አንዳንዶቹ ማስታወሻዎች የተጻፉበት ቀን ተገልጿል፤ በርካቶቹ መቼ እንደተጻፉ ግን አልተገለጸም፡፡ቀኑ ቢገለጽ በጊዜው ስለነበረው አጠቃላይ ሁኔታ እንድናውቅና ሌሎች ተዛማች ክስተቶችን እንድናሰላስል ይጋብዘን ነበር፡፡
ሮዛ ታሪኩን በስራ ቦታዋና በስራ ባልደረቦችዋ ቋንቋ በማቅረብዋ አልወቅሳትም፡፡ ግልጽነቷንና ታማኝነቷን አበረታታለሁ፡፡ መሸፋፈኑና መደባበቁ ነው ክፉኛ የጎዳን፡፡ ቃላት የሚጠበቅባቸውን ነገሮችን የመግለጽ ሚና በአግባቡ እስከተወጡ ድረስ ነውር አይሆኑም ብዬ አምናለሁ። ሮዛ “ሩካቤ ስጋ”፣”ግብረ ስጋ”፣”ተራክቦ ስጋ”፣”የጭን ገረድ”፣”የከንፈር ወዳጅ”፣”እቁባት” ወዘተ የሚሉ በስራ ገበታዋ ላይ ፍጹም የማትጠቀማቸውን ማለዘቢያና ማሽሞንሞኛ ቃላትን በማስታሻዎቿ ውስጥ ብትጠቀም ኖሮ አስመሳይ ትሆንብኝ ነበር። አርታኢዋም ይህን ነጻነቷን ስላልነፈጋት ምስጋናዬ ይድረሰው፡፡ ስለቡና ቤት ህይወት እየተወራ ቃላትን ማሽሞንሞን የመጽሀፉን ጠቅላላ መንፈስ የሚያውከው ይመስለኛል፡፡
ሮዛ የአዋቂ መጽሀፍ ነው፤እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንዳያነቡት በሽፋኑ ላይ ተገልጿል። እንደ አደገኛ መድሀኒት ህጻናትና ታዳጊ ወጣቶች ከማይደርሱበት ቦታ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ግን ይህ በሽፋኑ ላይ መገለጡ አደጋውን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳው፣ የእለት ማስታወሻዎች በባህሪያቸው ቅጽበታዊ ስሜቶች በትኩስ ስሜት፣ በማያመዛዝን ህሊና እና በጥድፊያ ወደ ጽሁፍነት የሚቀየሩ ሰዋዊ ትዝብቶች እንደመሆናቸው፣ ‹‹ሮዛ›› በዚህ ስሜት ውስጥ ሆና የከተበቻቸው ማስታወሻዎች በአፍላ እድሜ ላሉ ወጣቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት አደጋው የትየሌሌ የሚሆንበት አጋጣሚ የሰፋ ነው። በመሆኑም በኔ ግምት የአርታኢው ሚና መሆን የነበረበት እነዚህን ስሜት ያናወጣቸው የግል ማስታወሻዎችን ማለዘብና ማስከን ብሎም ለአንባቢ የማይጎረብጡ፣ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ መነበብ የሚችሉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን አርታኢው አሳክቶታል ብዬ አላምንም፡፡
ምክንያቱም የመፅሐፉ ስሜት አንባቢ ዘንድ ሲደርስም ቢሆን የልብ ምትን የሚያፈጥን፣ የቡና ቤት ሁካታው የሚሰማ፣ ፈንጠዚያው ያልበረደለት ሆኖ ነው፡፡  መጽሀፉ ውስጥ በርካታ የፊደል፣የቃላትና የሀሳብ አለመጣጣም ስህተቶች አሉ፡፡አርታኢው “ሮዛ በተለያየ አይነት ስሜት ውስጥ ሆና በተለያየ ቅጽበትና ጊዜ የጻፈቻቸው ማስታወሻዎች ስለሆኑ እንደፈለገች በመዘባረቅ መጻፏንና ያም ከነስህተቱ ማለፉን አንባቢዎች ይወዱታል፤ይረዱታል” የሚል አቋም ቢይዝ እንኳን መሰረታዊዎቹን ስህተቶች ማረም ነበረበት፡፡ ለምሳሌ “ሊሊ ቂጦ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ሊሊን አንዳንድ ቦታ ላይ ሚሚ ሆና እናገኛታለን፡፡”የቤዛ አልፋና ኦሜጋ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ታሪኩ የሚከወንበት  ኦሜጋ ሆቴል አንድ ቦታ ላይ ኦሜድላ ሆቴል ተብሎ እናገኘዋለን፡፡” የሚልኪና የሹገር ማሚዎቹ አጭር የህይወት ታሪክ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ወይዘሮ ሳሮን በምን አስማት ቲና እንደምትሆን ግልጽ አይደለም፡፡ ምናልባት እነዚህ ስህተቶች አርታኢውን ሰነፍ ያስብሉት ይሆን እንጂ ጸሐፊዋን ክፉኛ የሚያስተቹ ናቸው ለማለት አልደፍርም፡፡
 በተለያየ ውጥንቅጥ ስሜት ውስጥ ሆነን ክስተቱን ለማስቀረት ብቻ እንዳሻን ስለምንጽፍ (ዲያሪ የመጻፍ ልምድ ካለን)በሌላ ጊዜ በተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነን ስንመለከታቸው እንዲህ አይነት ተራ፣አስቂኝና አዝናኝ ስህተቶችን እንደምንፈጽም ባልዘነጋውም አርታኢው የሮዛን ስህተቶች ማለፍ አልነበረበትም ባይ ነኝ፡፡ አርታኢው “የእለት ማስታወሻ ከነስህተቱ ነው የሚያምረው፤አለበለዚያ ለዛውንና ወጥነቱን ያጣል” የሚል አቋም ያለው አይመስለኝም፡፡ መጽሀፍ ላይ ሁሉም አይነት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡በቀጣይ እትሞች ላይ እነዚህ ስህተቶች እንደሚታረሙ እምነቴ የፀና ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 14 December 2013 12:32

ለቡጊ

በግሬ ጣራ መርገጥ
ሙዚቃ ሲጋልብ መውጣት መውረድ መፍረጥ
ዓይኔን ማገላበጥ
መርበትበት መንቀጥቀጥ
መላጋት መንገድገድ እንደሰከረ ሰው
የናፈቀኝ ይህ ነው፡፡
ተነስቼ ልዝለል
ቡጊ ቡጊ ልበል…
ቡጊ ቡጊ ቡጊ
    ከበሮ ሲያጋፍት ሙዚቃ ሲያናፋ
ልብሴን ጥዬ ልጥፋ
ልራቆት አብጄ
ልብረር ካለም ሄጄ
ሙዚቃ በጥላው ይምጣ ይሸፍነኝ
ሁሉንም ያስረሳኝ፡፡
እንደ እሳት ቦግ ቦግ
መውለብለብ መንተግተግ
መቃጠል መሞት ነው
ይህ ነው፣ ዳንሴ ይህ ነው፡፡
ልቤን ይነሳኛል
ዛር ይሰፍርብኛል
ልወርውር እጆቼን
    ሙዚቃን እንደ ኳስ ልለጋው በግሮቼ
ልዝለል ተነስቼ፤
ቡጊ ቡጊ ልበል
መሬት ልንከባለል
ልዝለል ጮቤ ልምታ
ያቃዠኝ አንዳፍታ፤
ቡጊ ቡጊ ቡጊ
ገብረክርስቶስ ደስታ

Published in የግጥም ጥግ

በሃዋሣ ላይ የትራፊክ አደጋ የደረሠበት የ”ኢትዮ-ምህዳር” ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ፤ በአሁኑ ሠአት በኮሪያ ሆስፒታል ከፍተኛ የህክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል፡፡ የህክምና ወጪው ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ ግን በጋዜጠኛው እና በቤተሠቡ እንዲሁም በቅርብ ወዳጆቹ ብቻ ሊሸፈን አልተቻለም፡፡ የሙያ አጋሮቹ ለህክምናው የሚያስፈልገው ገንዘብ እንዳይስተጓጐል በማሰብም ኮሚቴ አቋቁመው፣ በጐ ፈቃደኞችን በማስተባበር ገንዘብ እያሰባሰቡ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ድረስ 40ሺህ ብር ገደማ ተሰብስቦ ለህክምናው የዋለ ሲሆን ለቀጣይ ህክምና ደግሞ ከ180 ሺህ ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ታውቋል።
የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እንደሚሉት፤ በጐ አድራጊዎች እስካሁን ያሣዩት ድጋፍ የሚመሠገን ቢሆንም የታሠበውን ያህል ድጋፍ ግን አልተገኘም፡፡ ለዚህም ተጨማሪ የገቢ ማሠባብ ስራዎች የተጠመዱት፡፡ አትላስ አካባቢ የሚገኘው የ”ኦ ካናዳ” ካፌ፣ ባር እና ሬስቶራንት ባለቤቶች የገንዘብ ማሰባሰቡን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ያላቸውን ፍላጐት አሳይተዋል፡፡ ባለቤቶቹ ከአስተባባሪ ኮሚቴው ጋር በመሆን ታህሣስ 7 እና 8 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ሰአት ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከልዩ የእራት ፕሮግራም ጋር የፋሽን ሾው እና ሙዚቃን ጨምሮ በአይነቱ ልዩ የሆነ  የገንዘብ ዝግጅት አሰናድተዋል፡፡
ጋዜጠኛ ኤፍሬም ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነትና በኮሚኒኬሽን የት/ት ዘርፍ ከተመረቀ በኋላ ላለፉት አምስት አመታት በተለያዩ የሃገሪቱ ፕሬሶች ላይ ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ሠርቷል፡፡ ለጉዳት የዳረገው አደጋ ያጋጠመውም በዚሁ ሙያው  በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የተፈፀመውን ሙስና የሚያጋልጥ ዘገባ ማቅረቡን ተከትሎ፣ የጋዜጣው አዘጋጆች ለተመሠረተባቸው ክስ አስረጂ ሊሆን ወደ ሀዋሣ በተጓዘበት ወቅት ነበር፡፡
በኮሪያ ሆስፒታል ከፍተኛ የህክምና ክትትል እየተደረገለት ከሚገኘው ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ጋር በጤንነቱና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አጭር ቃለ ምልልስ አድርገናል፡፡ ጋዜጠኛው ከህመም ስሜቱ ጋር እየታገለ በተዳከመ እና በተቆራረጠ ድምፅ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡


ጤንነትህ አሁን እንዴት ነው?    
አሁን ምንም አልልም … ከቀዶ ጥገናው በኋላ አንደኛው ሣንባዬ ላይ ጉዳት ደርሶብኝ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም በኢንፌክሽን ምክንያት ሣንባዬ በጣም ተጐድቶ ነበር፤ ግን መድሃኒት ስለተሠጠኝ አሁን ከዚህኛው ህመም አገግሜያለሁ፡፡
አሁን የሚሠማህ ምንህን ነው?
ከወገቤ በታች ምንም መንቀሣቀስ አልችልም። እግሬም ሠውነቴም መንቀሣቀስ አልቻለም። ጣቶቼም ላይ የመድከም ስሜት ይሠማኛል፡፡ ሠውነቴም ይደክማል፤ ከዚያ ውጪ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ፡፡
ሃኪሞችህ ስለ ጤናህ የነገሩህ ነገር አለ?
ያው እነሡ በየጊዜው ለውጥ አለሀ እያሉኝ ነው። ሁሌም እየመጡ ጤንነቴን ይፈትሻሉ፡፡ ሣንባዬም በፊት በኒሞኒያ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ነበር ጉዳት የደረሠበት፤ አሁን ግን ደህና መሆኑን ነግረውኛል፡፡
በቀጣይስ ምን አይነት ህክምናዎች ይደረጉልሃል?
እንግዲህ ፊዚዮ ቴራፒ ትንሽ ትንሽ ጀምሬያለሁ። ይኸው ህክምና የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡ ሌሎች ተከታታይ ህክምናዎችም አሉ፡፡ በቶሎ አገግማለሁ ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በጋዜጠኝነት ስራህ ላይ ሣለህ ነው ጉዳቱ የደረሠብህ፡፡ እንደው ከሙያው ጋር በተያያዘ የፈጠረብህ ስሜት?
ጋዜጠኝነት መርጬው የገባሁበት ሙያዬ ነው። በጋዜጠኝነት የራስህ ህይወት የለህም፡፡ በገንዘብ ያገኘሁት ትርፍ የለም ነገር ግን ለህዝቡ የሠናፍጭ ቅንጣት ታክልም ቢሆን በሙያዬ አበረክታለሁ ብዬ የገባሁበት ነው፡፡ በዚህ ህይወት ውስጥ ስትኖር እንደዚህ አይነት ነገሮች በኔ ላይ ይከሠታል ብለህ ባታስብም ይከሠታሉ፡፡ በሌሎች ሃገሮች እኮ ከዚህ በበለጠ ጠንካራ ሪፖርት የሚሠሩና በሙያቸው ላይ መስዋዕትነትን እስከ መጨረሻው የሚቀበሉ አሉ፡፡ እናም ጋዜጠኝነትን ስማርም ሆነ ወደ ስራው ስገባ ከዚህም የባሡ ብዙ ፈተናዎች እንደሚኖሩ አስብ ነበር፡፡
ድነህ ስትነሣ በሙያህ ትቀጥላለህ?
አዎ! እቀጥላለሁ፡፡ ሌላም ምርጫ የለኝም። የተማርኩትም ሆነ የልቤ ፈቃድ የሆነው ጋዜጠኝነት ብቻ ነው፡፡ እኔ ዝም ብዬ ቁጭ ልበል ብልም አይሆንልኝም፤ ሣልፅፍ መኖር አልችልም፡፡ ጋዜጠኝነት ደግሞ ራሱ ልትላቀቀው የማትችለው ሱስ ነው፡፡ ብዙ እያጣህበትም ቢሆን ሣትላቀቀው የምትኖርበት ሙያ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶ ጤንነቴ ከተመለሠ የምኖርበት ብቸኛው ሙያዬ ነው፡፡
ጋዜጠኞች (የሙያ አጋሮችህ) አንተን ለመርዳትና አለንልህ ለማለት እየተንቀሣቀሡ መሆኑን ታውቃለህ?  
አዎ! አውቃለሁ፡፡ በእውነት የሙያ አጋሮቼም ሆኑ ከጐናቸው የተሠለፉ አካላትን በሙሉ ምን እንደምል አላውቅም፡፡ ጋዜጠኝነት እንግዲህ ወገን ታፈራበታለህ ማለት ነው፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ይህን አሣይቶኛል፡፡ ማድረግ የምችለው ለተደረገልኝ ሁሉ ምስጋናዬን ማቅረብ ብቻ ነው። እንዲሁም የሙያ አጋሮቼን የበጐነት እንቅስቃሴ ተመልክተው ከጐኔ ለተሠለፉ ባለሃብቶችና ወዳጆቼ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ከዚህ በተሻለ ከጉዳቴ አገግሜ የበለጠውን ምስጋና እንዳቀርብ ደግሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን፡፡  
ህክምናህ እስከመቼ ይቆያል?
አላወቅሁም ግን ከእግዚአብሔር ጋር ብዙም የሚቀረው አይመስለኝም፡፡
የምታስተላልፈው መልዕክት ካለህ…  
ለጋዜጠኞችና ለአሣታሚዎች፣ በኔ ላይ የደረሠው አደጋ በነሡ ላይ እንደደረሠ ተሠምቷቸው ከጐኔ ለሆኑት ሁሉ፣ በተለይ ህይወቴን ለማትረፍ ርብርብ ላደረጉት የኮሚቴው አባላት፣ እግዚአብሔር ውለታችሁን ይመልስልኝ ከማለት ውጪ ሌላ ምን እላለሁ ብለህ ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ

ለረዥም ዓመታት በውትድርና ዓለም ውስጥ ነው የቆዩት፡፡ በጤና እክል ከወታደር ቤት ከተገለሉ በኋላ በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀመሩ፡፡ ነፃ ፕሬስ ሲጀመር በዋናነት ካቋቋሙት ሰዎች አንዱ ነኝ የሚሉት የ65 ዓመት አዛውንት በተለያዩ የግል ጋዜጣች ላይ ለ11 ዓመት እንደሰሩ ይናገራሉ፡፡ አዛውንቱ ከ20 በላይ መፃህፍትን ተርጉመዋል - በስማቸው ባይወጣም፡፡ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ግን በገጠማቸው ድንገተኛ ችግር ጐዳና ላይ ወደቁ። ማዕከሉ ታህሳስ 13 በግሎባል ሆቴል የሚያደርገውን የገቢ ማሰባሰብ ስራ አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ አዛውንቱን በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አግኝታ አነጋግራቸዋለች፡፡ ለመሆኑ ለጐዳና ያበቃቸው ችግር ምንድነው?

አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? ራሳቸውን በማስተዋወቅ ይጀምራሉ፡- ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ እባላለሁ። ትውልድና እድገቴ በሰሜን ሸዋ ዋና ከተማ ደብረብርሃን ነው፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም እዚያው ደብረብርሃን ነው የተማርኩት፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰድኩ በኋላ በዛን ወቅት ሀረር ሚሊታሪ አካዳሚ ይባል የነበረው ማሰልጠኛ ሶስት አመት ተምሬ ዲፕሎማዬን አግኝቻለሁ፡፡ ማሰልጠኛው የአካዳሚም የሚሊታሪም ትምህርት ነበረው፡፡ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ሀረርጌ ተመደብኩኝ፡፡ እስከ 1969 ሀረርጌ ነው የቆየሁት፡፡ የሶማሊያ ጦርነት ሲመጣም እዚያው ነበርኩኝ፡፡ የሶማሊያ ውጊያ ላይ ዘምቼ፣ ተዋግቼ ከጨረስኩ በኋላ የሻለቃነት ማዕረግ ተሰጥቶኝ ወደ ሰሜን ዘመትኩኝ፡፡ ሰሜን ለብዙ አመታት ቆይቼ በጥይት ዘጠኝ ቦታ ተመትቼ ነው የወጣሁት፡፡ ዘጠኙ ጥይት ምንዎት ላይ ነው የመታዎት? አብዛኛው እግሬ ላይ ነው የመታኝ፡፡ ክንዴም ላይ ተመትቻለሁ፡፡ ጀርባዬ ላይ የጥይት ፍንጣሪ አለ፡፡

ዋናዎቹና አብዛኞቹ አግሬ ላይ ያሉት ናቸው። እስካሁን ሁለት ጥይት በውስጤ ሳይወጣ አብሮኝ እየኖረ ነው፡፡ ከውትድርናው ዓለም የወጡት መቼ ነው? በ1981 ዓ.ም ነው የወጣሁት፡፡ የወጣሁበት ምክንያትም እነዚህ በውስጤ ያሉት ጥይቶች በጤናዬ ላይ ባስከተሉት ችግር የተነሳ ነው፡፡ ብዙ ሰው የሚያውቅዎት በጋዜጠኝነትና በትርጉም ስራ ነው፡፡ እስኪ ከውትድርና ከወጡ በኋላ የነበረዎትን ህይወት ያጫውቱኝ? ከሚሊታሪ ቤት ከወጣሁ በኋላ ለሁለት ዓመት አንድ ድርጅት ውስጥ ስርቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ነፃው ፕሬስን ካቋቋሙት ውስጥ አንዱ እኔ ነበርኩኝ። አሁን ከማስታወሳቸው እንኳን አዲስ አድማስና ሪፖርተር ጋዜጦች ይገኙበታል፡፡ ሌሎችም ነበሩ፡፡ አሁን ገበያው ላይ የሌሉ ማለቴ ነው፡፡ በአጠቃላይ በጋዜጠኝነት ለ11 ዓመታት ሰርቻለሁ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የሰሩት የትኛው ጋዜጣ ላይ ነበር? ኢትኦጵ ላይ ነው በመጨረሻው ሰዓት እሰራ የነበረው፡፡ በ1997ቱ ምርጫ ኢትኦጵም አባይ ጋዜጣም ታገዱ፡፡ እኔም ከጋዜጠኝነቱ ወጣሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ትርጉም ስራ ገባሁ፡፡ ከ20 በላይ መፃህፍት መተርጐምዎን አውቃለሁ። አንዱም ግን በስምዎት ሲወጣ አላየሁም፡፡ ለምን ይሆን? ከተረጐሟቸው መፃህፍት ውስጥ አንድ ሁለቱን ቢጠቅሱልኝ… ይህን ጉዳይ እንደምታውቂ አውቃለሁ፡፡

ከ20 በላይ መፃህፍትን ተርጉሜያለሁ፤ የወጡት በሌላ ሰው ስም ነው፡፡ ይህ የሆነው በስምምነት ነው። ይህንንም ለማንም ላልናገር ምዬ ተገዝቼአለሁ። አሁንም ምህላዬን አላፈርስም፡፡ የመጽሐፉን ስም ከጠቀስኩ መሀላዬን አፈረስኩ ማለት ነው፡፡ ይህንን ደግሞ አላደርግም፡፡ እሱን ይነግረኛል ብለሽ አትድከሚ፡፡ ዋናው እውነታውን ማወቅሽ ነው። አሁን አንድ የዲቴክቲቭ መጽሐፍ እየተረጐምኩ ነው፤ እሱ በስሜ ይወጣል፡፡ ይህ ማዕከል ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ነው፡፡ እርስዎ ትዳርና ቤት ነበረዎት፡፡ እንዴት ወደዚህ ማዕከል ሊገቡ ቻሉ? (በትካዜ ረዘም ያለ ጊዜ ወሰዱ) ልክ ነው፤ ትዳርና ቤት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን 2004 ዓ.ም ላይ ባለቤቴ በስኳር ህመም ተሰቃይታ ሞተች፡፡ ይገርምሻል፤ ከእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ት/ቤት በአካውንቲንግ ተመርቃ፣ ሥራ ስፈልግላት ነው ያረፈችው፡፡ በዚህ ምክንያት ጭንቅላቴ ተረበሸ፡፡ ባለቤቴ ለእኔ ሚስቴ ብቻ ሳትሆን ጓደኛዬም መካሪዬም ነበረች፡፡ ለእኔ ሁሉ ነገር ነበረች፡፡ አንዳንዴ ሁለመናሽን ስታጪ ይጨልምብሻል አይደለም? በዚህ ምክንያት ከአንድ አመት በላይ ራሴን አላውቅም ነበር፡፡

መቄዶኒያ በምን ሁኔታና የት ነው ያገኘዎት? አውቶቡስ ተራ አካባቢ ላስቲክ ቤት ውስጥ ወድቄ ነው የቆየሁት፡፡ ከዚያም ይህ ድርጅት በአንዲት ተማሪ ጠቋሚነት አንስቶ አመጣኝ፡፡ እዚህ ከመጣሁ በኋላ ለማገገም ሁለት ወር እንኳን አልወሰደብኝም፡፡ የድርጅቱ መስራች አቶ ቢኒያም “መጽሐፍ እንደምትተረጉም እናውቃለን፣ አሁን ጥሩ መጽሐፍ ፈልገህ ተርጉም፤ ድርጅቱ ያሳትምልሃል” አለኝ፡፡ ከዚህ በኋላ አዕምሮዬን ለማስተካከል አማኑኤልም አልሄድኩም፤ ምን አለፋሽ ይሄ የቢኒያም ቃል ብቻ ለወጠኝ፡፡ በውስጤ እንዲህ የሚል ሃሳብ መጣ፡፡ ማንም ሰው በህይወቱ ሊወድቅ ይችላል፤ መጥፎው ነገር ግን ወድቆ መቅረቱ ነው አልኩኝ፡፡ ይህ ሃሳብ ሞራሌን ከፍ አደረገውና አሁን መጽሐፍ መተርጐም ጀምሬያለሁ፡፡ መጽሐፍ መተርጐም ብቻ ሳይሆን በድርጅቱ ፋይናንስ ክፍል ውስጥ ሃላፊነት እንደተሰጠዎትም ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው፤ ሃላፊነቱን ወስጄ በጥሩ ጤንነትና መንፈስ እየሰራሁ ነው ያለሁት፡፡ ለድርጅቱ የሚገቡትን እርዳታዎች በደረሰኝ እረከባለሁ፡፡ ከትዳርዎት ልጆች አላፈሩም? ዋናው የአዕምሮዬ መናወጥ እርሱው ነው፡፡ ባለቤቴ ስትሞት ጐዳና የወጣሁት ልጆች ስለሌሉኝ ነው፡፡ ልጆች ቢኖሩ አጽናንተው ደግፈው ያኖሩኝ ነበር፡፡ በህይወቴ ውስጥ ከባለቤቴ ሌላ ማንም አልነበረኝም፡፡

እርሷ ስትሞት ቤቴንም እንዳማረበት ነው ትቼው የወጣሁት፡፡ አሁን ቤትዎ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ፣ ማን እንደሚኖርበትስ ያውቃሉ? የባለቤቴ ዘመዶች እንደሚኖሩበት ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ወደዛም መመለስ አልፈልግም፤ እሱን እያሰብኩ መጨነቅም አልፈልግም፡፡ አሁን በሰላማዊ ቦታና በጥሩ መንፈስ ነው ያለሁት፡፡ የባለቤትዎ ዘመዶች አይጠይቁዎትም? አንድ ሌላ ቦታ የነበረች እህቷ ብቻ በኢቢኤስ ላይ አይታኝ መጥታ ጠይቃኛለች፡፡ ስለ ሌሎቹ ምንም ለማለት ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡ እስካሁን መጥተው አልጠየቁኝም፤ እኔም አልጠብቅም፡፡ አሁን እየተረጐሙ ያሉት መጽሐፍ ርእሱ ምንድነው? አሁን የመጽሐፉን ስም ይሄ ነው ማለት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ቀደም ብዬ የተረጐምኳቸው መጽሐፎች የወንጀል ክትትል ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ ታውቂያለሽ፡፡ አሁንም በወንጀልና ክትትሉ ዙሪያ ያተኮረ ነው፡፡ የመጽሐፉን ስም ተተርጉሞ ሲያልቅ እንደርስበታለን፡፡ መጽሐፉን መቼ እንጠብቅ? ከሶስት ወር በኋላ ይወጣል፡፡ ያኔ ሰው እንዲገዛኝ በማስተዋወቅ ትረዱኛላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔም ጥሩ አድርጌ ለማቅረብ በደንብ እየተጋሁ ነው፡፡

ቀደም ሲል ሲጋራ እንደሚያጨሱ፣ መጠጥ እንደሚጠጡም ይታወቃል፡፡ አንዳንዶች ህይወትዎ ያልተለወጠው በሱስዎት ምክንያት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? ይህን ሀቅ ማንሳቱ ለሌሎችም ትምህርት ይሆናል፡፡ በነገርሽ ላይ በዛን ወቅት እጠጣ የነበረው በአጠቃላይ ህይወቴ እበሳጭ ስለነበር ነው፡፡ ብዙ አልጠጣም ግን በውስጤ ብስጭት ስለነበር በትንሹ እሰክራለሁ፡፡ ሲጋራ ለ37 አመታት አጭሻለሁ። አሁን መጠጡም ሲጋራውም ተረት ሆኗል፤ አልጠጣም አላጨስም፡፡ በዚህ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ አሁን ወዝዎት ግጥም ብሎ ወጣት ሆነዋል፡፡ ይታወቅዎታል? እንዴታ! አሁን ጤነኛና ደስተኛ ነኝ፡፡ ወፍሬ አታይኝም እንዴ! እኔ አሁን ተረጂ ሳልሆን በድርጅቱ ውስጥ ሰራተኛ ነኝ፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ለድርጅቱ በአይነትም ሆነ በጥሬ ገንዘብ ሲመጣ ደረሰኝ ቆርጬ እቀበላለሁ፡፡ ጐብኚዎች ሲመጡ ስለ ድርጅቱ መረጃ እሰጣለሁ፤ እንደ ህዝብ ግንኙነትም ያደርገኛል ማለት ነው፡፡ ወደ ሚዲያው ተመልሰው የመፃፍ ሃሳብ የለዎትም? እሱን አላወቅሁም፡፡ በትርጉሙ እቀጥላለሁ፡፡ ጋዜጦች ላይ ለመፃፍ ግን ወደፊት አመቺ ሁኔታዎች ይኖሩ እንደሆነ አላውቅም፡፡ አሁን ላይ ለመናገር እቸገራለሁ፡፡ እስኪ ወደ ጦር ሜዳ ውሎዎ ልመልስዎትና ትንሽ ያጫውቱኝ… መቼም ዘጠኝ ጊዜ ተመትቶ መትረፍና ለማውጋት መብቃት እድለኝነት ነው… ስለ ጦር ሜዳ ውሎ ካነሳን ከ1969 ዓ.ም እጀምራለሁ፡፡ ሀረርጌ ከአንበሳው ክ/ጦር ጋር ነው የነበርኩት፡፡ ከዚያ ከሶማሊያ ጋር ነው የተዋጋነው፡፡ በጣም ከባድ ውጊያ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ሰራዊት አልነበረንም፤ ሚሊሺያው ገብቶ መሰልጠን ነበረበት፡፡ እንደገና መድፈኛም ከኩባ መምጣት ነበረበት፡፡ አውሮፕላኖችም መለወጥ ነበረባቸው፡፡ ይሄ ሁሉ ችግር ነበር በወቅቱ፡፡

ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ ሰልጥና፣ የእኛን ደካማ ጐን ነበር የምትፈልገው፡፡ ወቅቱ ሀይለስላሴ ወርደው መንግስቱ ሲመጣ ስለነበር፣ ግርግር ነው፡፡ ሶማሌያም ይህን ክፍተት አይታ ነው የመጣችው፡፡ በአንድ ጊዜም ሀረርጌንና ጅጅጋን አስለቅቃናለች፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ኖሮም ሱማሊያ ድባቅ ተመትታ ነው በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀው፡፡ እንዴት ነው ያሸነፋችሁት? ሚሊሻውን በማሰልጠን እና በመሳሰሉት… ብቻ በአገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ሀይላችንን አጠናክረን፣ በመልሶ ማጥቃት ሽንፈትን ተከናንባ ልትሄድ ችላለች፡፡ እስኪ ስለሰሜኑ ውጊያ ያጫውቱኝ… ወደ ሰሜኑ ስንዞር ውጊያው አንድ አይደለም። ይሄ ኮንቬንሽናል ነው፡፡ ያኛው (የሶማሊያው) የሰርጐ ገብ ውጊያ ነው፡፡ እንግዲህ በሰሜኑ በኩል ትዋጊያለሽ፣ ታሸንፊያለሽ ትሄጃለሽ፡፡ እኛ እንግዲህ ከሁመራ ጀምረን ነው ኤርትራ ግዛት እየገባንና እየተዋጋን የሄድነው፡፡ በመጨረሻ ከረንን ሁሉ ይዘን ከዚያ ናቅፋ በር ላይ ነው የተመታሁት፡፡ ውጊያው በዛን ጊዜ ከባድ ነው፡፡ ከባድ ከሚያደርጉት ውስጥ አንዱ ረጅም ርቀት በእግር መሄድ አለ፤ ሌሎችም ፈተናዎች ነበሩ፡፡ በአጭሩ ይሄን ይመስላል፡፡ አሁን እድሜዎት ስንት ነው? 65 አመቴ ነው፡፡ እኔ ገና ጐረምሳ ነኝ እያልኩ ነው፡፡ ጐረምሳ ስልሽ… ስራ ለመስራት ብዙ አቅም እንዳለኝ ይሰማኛል፡፡ አሁን ወደከተማ ይወጣሉ? በደንብ ነዋ! አሁን እግሬም ጤናዬም ደህና ነው፤ እየወጣሁ እመለሳለሁ፡፡ በአጠቃላይ ደህና ነኝ፡፡ እዛው መርካቶ ላስቲክ ቤት ውስጥ ወድቆ መቅረትም ይኖር ነበር፡፡ እኔ እድለኛ ነኝ፡፡ ከዚያ ወጥቼ አዕምሮዬ ወደ ቀድሞ ጤናው ተመልሶ፤ ለዚህ መብቃቴ ተዓምር ነው፡፡ አሁን እንዲህ በጤና መኖር ከጀመርኩ ዘጠኝ ወሬ ነው፡፡ በውትድርና ህይወትዎ በወቅቱ ከነበሩ ባለስልጣናት ጋር ምን አይነት ቅርርብ ነበረዎት? መልካም ቅርርብ ነበረኝ፡፡ በተለይ ከእነማን ጋር ይቀራረቡ ነበር? ጀነራል አበበ ገብረየስ ለምሳሌ በጣም ይቀርቡኝ ነበር፤ የማዕከላዊ አዛዥ ነበሩ፡፡ አሁን አሜሪካ ይኖራሉ፡፡

በነገራችን ላይ በውትድርና ህይወቴ የመረጃም ሰው ነበርኩ፡፡ ሀረር ሶስተኛ ክፍለጦር እያለሁ ሴኩዩሪቲ ኦፊሰር ነበርኩኝ፣ በዚህ ምክንያት ከሁሉም ጋር በስምምነት ነው የምኖረው፡፡ አንቺ የመረጃ ሰው ሆነሽ ፀባይ ካላሳመርሽ የመረጃ ድርቅ መታሽ ማለት ነው፡፡ አሁን ለጋዜጠኞች የሚሰጠው ኮርስ በዛን ወቅት ለመረጃ ኦፊሰር የሚሰጠው አይነት ነው፡፡ ጋዜጠኛ ሆነሽ መረጃ የምትፈልጊው ለህዝቡ ለማቀበል ነው፡፡ በሚሊታሪ የመረጃ ኦፊሰር ሆነሽ መረጃ የምትሰበስቢው ግን ለጦር ሰራዊቱ ለማቀበል ነው፡፡ ጋዜጠኝነትና በወቅቱ እኔ የምሰራው የመረጃ ስራ የስፋትና የጥልቀት ካልሆነ ልዩነት የለውም። ነገር ግን ጋዜጠኛ ሆነሽ አንድ በእውነታውና በዘገባው መካከል ልዩነት ያለው ነገር ብታቀርቢ እንደምንም ሊድበሰበስ ይችል ይሆናል፡፡ የመረጃ ኦፊሰር ሆነሽ ለጦሩ የምታቀርቢው መረጃ ከተለያየ መዘዝ ያመጣል፡፡ እንዴት? ለምሳሌ በወታደር ቤት ጠላት አንድ ሺህ ሆኖ ሳለ፣ አንቺ አምስት መቶ ነው ብትይ አገርሽን ገደል ከተትሽ ማለት ነው፡፡ አንቺም ዋጋ ትከፍይበታለሽ፤ ስለዚህ ጉዳዩ ሃይለኛ ነው፡፡ ረጅም ጊዜ ከወረቀት ጋር እንደማሳለፍዎ አይንዎት እንዴት ነው? አይኔ ጥሩ ነው፡፡ ሀኪም ያዘዘልኝ መነጽር አለ፤ ስሰራ እሱን እጠቀማለሁ፡፡ እርግጥ መነፅር ሳላደርግ ለማንበብ እቸገራለሁ፡፡ በሌላ ጉዳይ ግን አይኔ ደህና ነው፡፡ በመጨረሻ የምታመሰግኗቸው ሰዎች ካሉ እድሉን ልስጥዎት… እኔም በጣም አመሰግናለሁ፤ ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የዚህን ድርጅት መስራች አቶ ቢኒያምን እና በጐ ፈቃደኛ ሆነው እኛን የሚያገለግሉትን ሁሉ በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በአንድ ወቅት የአገር ባለውለታ የነበርን ሰዎች ነን መንገድ ላይ ወድቀን የነበርነው፡፡ አሁን ከየቦታው ተሰብስበን ቀሪ ዘመናችንን በደስታና በጤና እንድናሳልፍ ሆነናል፤ ደስተኞች ነን፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 14 December 2013 12:21

የባህር ዳር የጉዞ ማስታወሻ

“ለካ በራሳችን ራሳችንን መርዳት፣ ማሻሻል፣ መለወጥ እንችላለን አልን” አቶ አበበ ብርሌ

          በአውሮፕላን ባህር ዳር ከተማ ገብቼ ወደ ማረፊያዬ ሆቴል ሄድኩኝ፡፡ ባህር ዳር እንደወትሮው ሞቅ ደመቅ እንዳለች ናት፡፡ ከእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ድርጅት ተጠሪ ጋር ሆነን በመጀመሪያ እንድጐበኝ በተዘጋጀው ፕሮግራም መሠረት፤ ጐህ ለሁሉም ማህበረሰብ ልማት ማህበርን ለማየት ወደዚያው አመራሁ፡፡ ግሼ አባይ ቀበሌ ማህበር ካረፍኩበት ሆቴል ቅርብ ነው። የማህበሩን የሂሳብ ሹም አገኘሁ፡፡ ወደ ጽ/ቤታቸው እየሄድን የሠሯቸውን አንዳንድ ሥራዎች ለመቃኘት እየተዘዋወርን ነው። “ገቢ ማስገኛ ምን አላችሁ?” አልኩት፡፡ “ባጃጅና ለስላሳ ማከፋፈያ አለን” አለኝ፡፡

“ያቻትልህ ባጃጇ፡፡ ካፌም ልንከፍት ነው፡፡ አሁን ድሆች ሠራተኞችን ምልመላ ላይ ነን፡፡ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆች ላይ ነው የምናተኩረው፡፡ ይሄ የምታየው የት/ቤት ቅፅር ግቢ ከ1-6 ድረስ ትምህርት ማጠናከሪያ ነው፡፡ እናስተምራለን፡፡ መምህራኑ በዲግሪና በዲፕሎም የተመረቁ ናቸው፡፡ የተወሰነ የኪስ ክፍያ እንከፍላቸዋለን፡፡ ይሄኛው መጋዘናችን ነው፡፡ ቢራ፣ ለስላሳ፣ ወይን ጠጅ የምናከማችበት ነው፡፡ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ናቸው ሠራተኞቹ፡፡ ተቀጥረው ለኛ ትንሽ ገቢ እየሰጡ ራሳቸውን እንዲችሉ የምናደርግበት ነው፡፡ ያችኛዋ የፎቶ ኮፒና የህትመት ሥራ የሚሠሩባት ያከራየናት ክፍል ናት፡፡

ዛሬ እሁድ ስለሆነ የሉም እንጂ በደምብ ይሠሩባታል፡፡ እቺም የገቢ ማስገኛ ናት!” “የተቋማቋማችሁት መቼ ነው?” አልኩት፡፡ በ1995 መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ ጥር ጀምሮ ራሳችንን ችለናል - 2005፡፡ ሠርቶ ሠርቶ እየሩሳሌም ወጣ በቃ! አስረክበውናል!” ወደሌላ ቢሮ እያሳየኝ፤“እቺኛዋ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ያሉ አቻ ማህበራት ጥምረት ፈጥረን የምንሠራባት የጥምረት ቢሮ ናት፡፡ የጋራ ችግሮችን እንፈታባታለን፡፡” “አንተ ወደ “ጐህ ለሁሉም” እንዴት ገባህ?” “ያኔ ያካባቢውን ችግር ለመፍታት እየሩሳሌም ይንቀሳቀስ ነበረ፡፡ ማህበረሰቡንና ቀበሌውን ሰብስቦ ሲያወያይ፤ በኤችአይቪ ዙሪያ ተተኩሮ፣ እናት አባታቸውን ያጡ ህፃናትን ለመርዳት ምን እናድርግ ሲባል፤ ሰው ይመረጥ - ፍቃደኛ የሆኑ ተባለ፡፡ ተመረጥን፡፡ እኛ ገባን፡፡ ፋብሪካ ነበር ፊት የምሠራው! አሁን የማህበሩ የሂሳብ ሹም ሆኜ ነው ይሄን የህል ዓመት የምሠራ!” “የጐጃም ሰው ነህ?” “አዎ፤ ይቺኛዋ ደግሞ የልማት አመቻቾች ቢሮ ናት” አለኝ ወደሌላ ቢሮ እየጠቆመኝ፡፡ ጽ/ቤቱ ቢሮ ገባን፡፡ የሂሳብ ሹሙ ሰብሳቢውን ሊጠራ ፈጥኖ ሄደ፡፡ ሰብሳቢው መጡና መጨዋወት ጀመርን፡፡ * * * የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ አበበ ብርሌ ዝግ ብለውና አስረግጠው ከመናገራቸው ባሻገር መንፈሰ ምሉዕነትና ቅንነት ይታይባቸዋል፡፡ “እስቲ ስለ ሁሉ ነገራችሁ እናውራ - ያጫውቱኝ” አልኩ፡፡ “አበበ ብርሌ እባላለሁ - የጐህ ለሁሉም ማህበረሰብ ልማት ማህበር ሰብሳቢ ነኝ፡፡

መጀመሪያ ማህበራችን ሲመሰረት በዚሁ በግሼ አባይ ቀበሌ ሶስት ቀበሌዎች ነበሩ፡፡ ራሳቸውን የቻሉ ልማት ማህበሮች ተመሰረቱ፤ በ95 መጨረሻ፡፡” “እንዴት?” “በተለይ ይህ ቀበሌ ቀደምት ነው - የባህር ዳር ከተማ ሲመሠረትና ሲጀመር ገበያው ሳይቀር የነበረ ነው፡፡ ገበያውን ተከትሎ ህዝቦች የሠፈሩበት ሲሆን አሁን ግድ ባህርዳር እየተለወጠችና እየተሻሻለች በመጣችበት ሁኔታ ላይ፤ አዲስ ቀበሌዎች የራሳቸውን ግንባታ እየገነቡ ሲወጡ፣ እዚህ ያለው ምንም አማራጭ የሌለውና በቀበሌ ቤት የሚኖር እጅግ ደሀ የሆነ ሰው ብቻ ስለቀረ፣ ከዚህም ውስጥ በኤች አይ ቪ ፣እናት አባት ያጡ ህፃናት ነበሩና ምን ይሁኑ ሲባል፤ ቁጥራቸውም ከፍ እያለ በመሄዱ፤ ይህንን ሁኔታ ከህብረተሰቡ ጋር ሆኖ ችግሩን ለመፍታት፣ ሊቋቋም ችሏል፡፡” “እየሩሣሌም ድርጅትስ ያኔ እዚህ ነበር እንዴ?” “እየሩሳሌም ድርጅት መጀመሪያ በእኛ ውስጥ አልነበረም። የነበረው ቀበሌ 12 ላይ ነው፡፡ የቀበሌውን አቅም እየገነባ ህዝቡ እየተረባረበ ነበር፡፡ ያንን ስናይ ለካ በራሳችን ራሳችንን መርዳት፣ ማሻሻል መለወጥ እንችላለን አልን፡፡ የራሳችንን ችግር በራሳችን ለመፍታት ይቻላል፤ አልን፡፡ አመንን፡፡ ያለምንም ደጋፊ አካል መቋቋም ጀመርን። የእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (እህማልድ) ወደኛ መምጣት ጀመረ፡፡

ታሪካዊ አመጣጡ ማህበረሰቡ ቀበሌ 12 ዕድገት እያሳየ ነበረና መንፈሳዊ ቅናት ፈጠረ፡፡ እኛም‘ኮ የበለጠ ለመንቀሳቀስ እንችላለን ተባባልንና ስብሰባ ተጠራ አለቀ፤ ተመረጥን፡፡ ለበጐ አድራጐት ተመረጥን። 7 ሥራ አስፈፃማዎች መጣን፡፡ ተመሠረተ፡፡ ትኩረታችን ወላጅ ባጡ ህፃናት ላይ ነው፡፡ አንድ አመት ቆየን መዋጮ ለማዋጣት እየሞከርን፡፡ በተለይ ልጆቻቸው ሞተው የተቀመጡ ሰዎች አሉ። የልጅ ልጅ ይዘው የቀሩ አሳዛኝ ሰዎች አሉ፡፡ የልጅ ልጅ ይዘው ራሳቸውን እንኳ ማስተዳደር የማይችሉ ምስኪን አያቶች አሉ። ከአያትና ከጐረቤት ጋር የሚኖሩ 23 ልጆች መርጠን ተነሳን። የአመራረጣችን መስፈርት ምንድን ነው? ሁለቱንም ያጡ፣ አንደኛውን ያጡ፣ እያልን ነው፡፡ ከዛ እየሩሳሌም መጣ 4 ፕሮግራሞችን ይዞ!” “ምን ምን?” “ወላጅ ላጡ ህፃናት ድጋፍና እንክብካቤ፣ ከዛ በትምርት ዘርፍ፣ ቀጥሎ የጤና፣ ከዛ የከተማ ግብርናና የኑሮ ማሻሻል!! ያን ይዘን ፕሮግራሙን ማስኬድ ጀመርን፡፡ ፕሮግራሙን ማስኬድ ማለት እንዴት ነው? ከ1-6 የሚማሩትን ከመንግሥት ት/ቤት ብቻ መርጠን ማጠናከሪያ እንዲያገኙ አደረግን፡፡” “ለምን ከመንግሥት ት/ቤት ብቻ?” አልኳቸው፡፡ “ምክንያቱም በመንግሥት ትምህርት ቤት በነፃ የሚማሩት አብዛኞቹ ገንዘብ የመክፈል አቅም የሌላቸው ስለሆኑ፤ የእኛ ዓላማና ትኩረት ደግሞ፤ የተቸገሩትን ለይቶ መርዳት ስለሆነ፤ እነሱን ብቻ አጥርተን ወስደን ነው ማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ ያደረግነው፡፡

መጠናከሪያ ት/ቤቶችን፣ በየቦታው በቀርክሃ የተሠሩ ሼዶችን፣ የጥላ ከለላ ት/ቤቶችን ሠራን፡፡ የተማሪዎች በተለያየ ቦታ መቀመጥ የመቆጣጠር ችግር ስለፈጠረብን ወደ አንድ ትልቅ ሼድ ባንድ አካባቢ ባንድ ጥላ ጠቅላላ ሥር አደረግናቸው፡፡ ቀበሌውና መስተዳድሩ አንድ ቦታ ሰጠን፡፡ እየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ደግሞ ክፍሎቹን ሠራልን፡፡ ከ1ኛ -6ኛ ክፍል የዲግሪና የዲፕሎማ ደረጃ ባላቸው መምህራን የትምህርት ማጠናከሪያ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ በሚያርፉበት ፈረቃ ነው መጠናከሪያው የሚሰጣቸው፡፡” ቅንጅቱ ገረመኝ፡፡ መንግሥት፣ እየሩሳሌምና ማህበረሰቡ! “ጤናም አለ፡፡ ያካባቢ ንጽህና ኮሚቴ አቋቁመን በቡና ጠጡ ፕሮግራም ከእየሩሣሌም በሚደረግንል ድጋፍ በሣምንት አንድ ቀን፤ በየሠፈሩ፣ በየተራ ይጠራሉ፡፡ እዛ ላይ ስለ ኤች አይ ቪ፣ ስለተላላፊ በሽታዎች፣ ስለ አካባቢ ንጽህና፤ ትምህርት ይሰጣል፡፡ በራሪ ጽሑፎች ይነበባሉ፡፡ ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ ቤቶች ውስጥ ላሉ አቅመ ደካማ አረጋውያን ፤ ሊፈርሱ የደረሱ ቤቶች እንዲታደሱላቸው ይደረጋል፡፡ በክረምት የሚያፈሱ፣ በበጋ ፀሐይ የማይከልሉ ቤቶች ከቀበሌው ጋር ዞረን መርጠን ነው። እስካሁን ወደ 17 ቤቶችን ጠግነናል፡፡ ባለ 8 ክፍል ሻወር ቤት ሠርተናል። ለጤና ጠቃሚ ነው፣ ገቢም አለው፡፡ ባካባቢው ካሉት ዝቅ ባለ ዋጋ ለችግረኛው ማህበረሰብ ሲባል፤ ያገለግላሉ፡፡ መፀዳጃ ቤትም ገንብተናል፡፡ በተለይ የኛ ማህበረሰብ የገነባውን ሽንት ቤት ልዩ የሚያደርገው፤ አካል ጉዳተኞችንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ነው! ለምሳሌ በዊል ቼር በቀጥታ ሊገቡ የሚችሉበትና መቀመጪያውም ለነሱ በሚያመች ተጠንቶ የተሠራ መሆኑ ነው። ህብረተሰቡ ተራ በተራ እያፀዳ ንጽህናውን ይጠብቃል፡፡ የኑሮ ማሻሻያና የከተማ ግብርናም እንደዚሁ፡፡

“የኑሮ ማሻሻያ ማለት ምን ማለት ነው” አልኳቸው፡፡ “ለምሳሌ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑትን ሴቶች በማነቃቃት ብድር በመስጠት በተዘዋዋሪ ፈንድ መደገፍ ነው፡፡ የኑሮ ማሻሻያ ይሄው ነው፤ ሌላ ትርጉም ነገር የለውም፡፡” አሉኝ ፍርጥም ብለው፡፡ “ደሞ ኑሯቸው በእርግጥ ተሻሽሏል እልሃለሁ!” በከተማ ግብርናም በኩል፤ ባለቻቸው ቦታ ላይ ዶሮ፣ በግ እንዲያረቡ ሆነዋል፡፡ በእየሩሣሌም በኩል ይሰለጥናሉ። እኛ መልምለን እንልካለን፡፡ በእርግጥ በመሥፈርት ነው፡፡ ትኩረታችን ሴቶች ላይ ነው፡፡ ከዚያ የዶሮ ቤት እንዲሠሩ እገዛ ይደረግላቸዋል። ሚስቶቻቸው የሞቱ ልጆች ይዘው ቀርተው ያሉ ወንዶችም አሉ፡፡ እነሱንም፣ ሚስቶቻቸውንም እንደግፋለን። በእርግጥ በዚህ በኩል ጥሩ ሁኔታም ይታያል፡፡ ደካማ ጐንም ይታያል፡፡ ለስላሳ፣ ቢራ፣ አምቦውሃ እናከፋፍላለን፡፡ አሁንም በዝቅተኛ ዋጋ ለዝቅተኛ አከፋፋዮች፡፡ እነሱም እኛም እንጠቀማለን፡፡ አንዲት የሻይ ክበብ ሠርተናል፡፡ ዓላማችንን አንስትም አየህ፡፡ 3 ወጣቶች ሴቶች ሥራ የሌላቸው መልምለን ሥራ ማስያዝ ነው፡፡ ራሳቸውም ፈጠራ ጨምረው ከኛ ተረክበው እየሸጡ ራሳቸውን መቻል ነው ትልቁ ነገር!! ሌላው ጄክዶ - ሲዳ የገዛልን ባጃጅ ናት። እሷ አሁን በቀን 100 ብር ታስገባለች፡፡ የህዝቡ መዋጮም አለ፡፡ ገና ስንነሳ ያለን አላማ!!” “ትዘልቁ ይመስላችኋል?” “እርግጥ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ በጣም ሰፊ ነው። እንደውም ያኔ እየሩሳሌም ከጐናችን ባይቆም ኖሮ እምንዘልቀው አይሆንም ነበር፡፡

ሁለተኛ፤ የበጐ ፈቃደኝነት ስሜት ደሞ በጣም ያጥራል፡፡ ምርጫ ስናደርግ “እኛ በቃን ስንል፤ “እንዴ እናንተ ከለቀቃችሁማ ማህርበረሰቡና ገንዘቡ የትም ይውደቁ ማለታችሁ ነው ወይ” ይላሉ፡፡ ይሄ ግን በእኛ ስንረዳው ሁለት መልዕክት አለው (1) ምናልባት ከልብ የምንሠራውን ሥራ ተቀብለውት አምነውበት ሊሆን ይችላል (2) ሌላ ትንሽ የማይባለው ቁጥር፤ ምናልባት ቆንጆ ብቃትና ችሎታ ያለው ሆኖ ወደዚህ ሃላፊነት ግባ እንዳይባል ሌላውን እየገፋፋ እኛን እዚሁ ቆዩ እንዲለን ያደርግ ይሆናል፤ የሚል ግምት አለኝ! በፍቅርና በእኛ ሥራ በማመን ብቻ ነው ያቆዩን የሚል ዕምነት የለንም! ሌሎችን ደሞ እንሞክር መባል አለበት፡፡ ዕውነት እንንገርህ ምንም ዓይነት የታክሲ የምን የምን የሚሰጥ ነገር የለም፡፡ ፈንድ ሲገኝ ለስልክና ለአንዳንድ ወጪዎች ማካካሻ ተብላ የምትሰጥ ሣንቲም አለች፡፡ ያ ከሌለ ያለምንም እንሠራለን፡፡ ጊዜው ሲረዝም ግን እየቀዘቀዙ መሄድ አለ፡፡ አመቻቾች ብዙ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ተዘዋዋሪ ብድር እንሰጣለን፡፡ ሆኖም እናጣራለን፡፡ ከሌላ አካባቢ ወስደው ቢሆን ገንዘቡ ወጥቶ መቅረት የለበትማ!” “የማኅበራት ጥምረት አላችሁ?” “10 ማኅበራት አሉ፡፡ ጐህ ለሁሉ ፀሐፊ ነው” “Experience Sharing (የልምድ ልውውጥ) እንዴት ነው?” “አዎ፡፡ አዳማ፣ ደብረዘይት፣ ድሬዳዋ፣ ወረታ፣ ሐሙሲት፣ እንድብር፣ ወልቂጤ… መዓት ነው የሄድንበት፡፡ የእየሩሳሌም ባህርዳር ፕሮግራም ጽ/ቤት፤ ቀበሌዎች፤ አቻ ማህበረሰብ፣ አንድ ላይ አቀላቅሎ ለልምድ ልውውጥ ይዞን ይሄዳል። የዕድሮችን ህብረት ቅንጅት ልዩ ልዩ ዘርፎችን እንቅስቃሴ በማየታችን እኛም ተጠቅመናል፣ እነሱም ተጠቃሚ ናቸው፡፡ “ግን በብዛት ጐጃም ሄደን ልምድ አግኝተናል ብለውኛል። ይሄ ልዩ ምክንያት ይኖረው ይሆን?” “እንደ ፕሮግራም ጽ/ቤቱ ጥናት ነው፡፡

አንዱ ጋ የጐለበተ ልምድ፣ ሌላ ጋ ደካማ ሊሆን በመቻሉ በፕሮግራም ተጠንቶ የሚኬድበት ነው፡፡” “ጄክዶ ብቻ ነው እናንተም መክራችሁ ትንቀሳቀሳላችሁ?” “እኛም አጥንተን ፕሮግራም ይዘን ፕሮጀክት እንቀርፃለን። አንዳንዴም ፕሮግራም ጽ/ቤቱ ራሱ ያዘጋጃል፡፡ የእኛን ፍላጐት መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ብዙ ድርጅቶች አሉን፡፡ ጄክዶ Phase out ካረገ በኋላ እኛ ነን የምንከታተላቸው ገንዘብም ምደባ ላይ እንሠራለን። ካፒታል አላቸው፡፡ ሂሳቡን የእኛ ማህበር ይሠራላቸዋል፡፡ ከራሳቸው መልምለው የሚሰጡንን መንግሥት እንዲያውቅ ይደረጋል። ወጣቶችን በሙያ እናሳድጋለን፡፡ ለምሳሌ አራት ወጣቶች በሹፌርነት አሰልጥነናል፡፡ የፀጉር ሥራ፣ የኤሌክትሪክ ጥገና፣ የምግብ ዝግጅት ሥልጠና እንዲያገኙ እንጥራለን፡፡ (ይቀጥላል)

Published in ባህል

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

       በፍጥነት ሚሊየነሮች በመፍጠር ‘ድፍን አፍሪካን ቀደምን’ ምናምን ነገር ተባለ አይደል! ይሁና…እንግዲህ ምን ይደረግ! ነገርዬውማ… “ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ…” ሲባል እንደከረመው ይሄም ‘ማስፈንደቁ’ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አለ አይደል… በብዙ አሥርት ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ያጡ የነጡ ሰዎች በሞሉባት ሀገር፣ ሽቅብ ከመውጣት ቁልቁል መውረድ እጅግ በጣም በቀለለበት ዘመን…ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሚሊየነር አለ ተብሎ…ዓለም ድንቃ፣ ድንቅ መዝገብ ላይ አስፍሩን አይነት ነገር ቀሺም ነው፡፡ እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሁሉም ነገር ከገንዘብ ጋር እየሆነላችሁ ነው፡፡ ‘ፈረንካ’ ከኦክሲጅንም በበለጠ ‘ለህይወት አስፈላጊ’ የሆነበት አገር እየሆነላችሁ ነው፡፡

ያለ ‘ፈረንካ’ የሚሆን ነገር እየጠፋ ነው፡፡ እኔ የምለው…“ለነፍስ ይሆነኛል…” ምናምን ተብሎ የሚሠራ ነገር ጠፋ ማለት ነው! ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ነፍሳችንን ‘ሉሲፈር’ በወለድ አግድ የያዘብን ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ…ከላይ እስከታች ነገረ ሥራችን ከሉሲፈር ጋር… ‘ውል ባፈርስ ያፍርሰኝ’ አይነት ነገር የተፈራረምን ያስመስልብናላ! እናማ ዘንድሮ…‘የስድሳ አራት ሺህ ብሩ ጥያቄ’ …አለ አይደል… “ምን ያህል ያውቃል?” ሳይሆን “ምን ያህል አለው?” ነው፡፡ ጠቅላላ…ከቤተሰብ ጀምሮ የግንኙነቶች ሁሉ ማስተሳሰሪያ ክሮች ሦስት ብቻ ሆነዋል – ገንዘብ፣ ገንዘብና ገንዘብ ብቻ! ስለ ገንዘብ ፍቅራችን ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ‘አንድ፣ ሁለት ለማለት’ ቡና ቤት ሲገባ አንድ ጓደኛው ብቻውን መጠጥ ይዞ ቆዝሞ ያገኘዋል፡፡ “ፊትህ በጣም ነው የተለዋወጠው፡፡ ምን ሆነሀል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ “እናቴ ሰኔ ላይ ሞተች” ይላል ሰውየው፡፡

“ለሀዘኔ ጊዜ እንዲሆነኝና እሷንም እንዳስታውስበት 10‚000 ዶላር ትታልኝ ነበር፡፡” “አሳዛኝ ነገር ነው፡፡” “ሐምሌ ላይ ደግሞ፣” ሲል ጓደኝየው ቀጠለ፣ “አባቴ አረፈ፡፡ ሆኖም እሱም 50‚000 ዶላር ትቶልኝ ነው ያለፈው፡፡” “በሁለት ወራት ሁለቱንም ወላጆች ማጣት በጣም ከባድ ነው፡፡ ብትቆዝምም አይገርምም፡፡” “ያለፈው ወር ደግሞ አክስቴ አረፈች፡፡ እሷም 15‚000 ዶላር ትታልኝ ነበር፡፡” “ሦስት የቅርብ ዘመዶች በሦስት ወር… በጣም ያሳዝናል!” ይሄን ጊዜ ሰውዬ ሆዬ ምን አለ መሰላችሁ… “በዚህ ወር ግን ድርቅ ብሏል፡፡ አንድ እንኳን የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!” ይኸውላችሁ…ዘመናችን እንዲህ… “የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!” አይነት ሊሆን እየተቃረበ ነው። የሁሉም ነገር አልፋና ኦሜጋ ገንዘብ እየሆነ ነው፡፡ ሁሉም ነገር “ከሌለህ የለህም…” እየሆነ ነው። ሁሉም ነገር “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ…” ነው፡፡ እናላችሁ… ስንት ሚሊየነሮች እንደተፈጠሩ ከምናውቅ ይልቅ ስንቶች ‘ከታች ወደላይ’ ወጡ የሚለውን መስማት እንፈልጋለን፡፡

እንዲህ ‘በቀላሉ’ ሚሊየነር ለመሆን የሚችሉ ካሉ… አለ አይደል… ምነው በቀን ሁለቴ ለመብላት፡ በዓመት አንድ ጨርቅ ለመለወጥ የሚታትሩት እንዳቃታቸው ምክንያቶቹ ቢነገሩን እንመርጣለን፡፡ እነ እንትና…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በቀይ የሎተሪ ትኬት እየሸወዳችሁ… “እሰይ፣ እሰይ… እግዜር ይስጥሽ…” እንዳላላችሁ ‘ነገርዬው’ አንደኛውን የቦረና ሠንጋ ዋጋ ሆኖላችሁ አረፈ አይደል! “የፕራይቬታይዜሽን ማመልከቻ ያስገባህ ነው የሚያስመስለው…” ያልከው ወዳጄ… “…ፎር ኤ ላውዚ ፋይቭ–ሚኒትስ!” ካለው ‘ፈረንጅ’ ጋር ተገናኝታችሁ ታውቃላችሁ እንዴ! አይ…ራሱ ‘ፋይቭ’ የተባለውም ‘የፍልሚያ ጊዜ’ አልረዘመም ወይ ብዬ ነው! ቂ…ቂ…ቂ… እናላችሁ… ሚሊየነሮችን በብዛት በማፍራት “አፍሪካን ቀደማችሁ…” የሚሉን አጥኚዎች…‘ስኮች ኦን ዘ ሮክስ’ እየገለበጡ እንዴት እንደሚሳለቁብን አይታያችሁም! (የፈረደበት ፌስቡክ ምናምን ገብታችሁ ስለ እኛና አገራችን የሚቀለዱትን ቀልዶች ብታዩ…የምር ‘ፈረንጆቹ’ ስለ እኛ የሚያስቡትን ታያላችሁ፡፡) እናማ… ወደላይ የወጡትን ሺህ አራት መቶዎችን ብቻ ሳይሆን ወደታች እየወረድን ያለነውን በርካታ ሚሊዮኖች ቁጥር ቢነግሩን አሪፍ ነበር፡፡ እግረ መንገዴን ይቺን ቀልድ ቢጤ ስሙኝማ… ሰውየው ሰባት ልጆች አሉት፡፡ በዚህም በጣም ከመኩራቱ የተነሳ ሚስቱን ሰው በተሰበሰበበት ቦታ እንኳን ሳይቀር… “የሰባት ልጆች እናት!” እያለ ይጠራት ጀመር፡፡

እሷ ደግሞ አጠራሩ ስላልተመቻት ብትቃወመውም ሊተዋት አልቻለም፡፡ ታዲያላችሁ…አንድ ቀን ምሽት ድግስ ተጠርተው አብረው ይሄዳሉ። አንድ ሰዓት ያህል ከቆዩ በኋላ ሰውየውም ደክሞት ወደ ቤት መመለስ ይፈልጋል፡፡ እናላችሁ…ቤቱ ውስጥ ያለው ሰዉ ሁሉ እየሰማ ጮክ ብሎ… “የሰባት ልጆች እናት፣ ቤታችን እንሂድ፣” ይላል። (የትኛውን ነገር የት ቦታ መናገርና አለመናገር እንዳለባቸው ከማያውቁ ሰዎች ይሰውራችሁማ!)” ታዲያላችሁ… የበሸቀችው ሚስት ሆዬ በበኩሏ፤ ጮክ ብላ ሰዉ ሁሉ እየሰማ ምን ብትለው ጥሩ ነው… “እሺ፣ የአራት ልጆች አባት!” ‘ዓሳ ጎርጓሪ…’ ይላችኋል የዚህ አይነቱ ነው፡፡ አሀ…የማይመለከተውን ሦስቱን ልጆች መጨመር የለበትማ! ቂ…ቂ…ቂ… (ስሙኝማ…በሽወዳ የተወለዱ ልጆች “ቁርጥ አባታቸውን” ይመስላሉ የሚባለው እውነት ነው እንዴ! አይ…አንዳንድ ወዳጆቼን የሚመስሉና ‘ሚስቶቻቸውን የማይመለከቱ’ ልጆች ያየሁ ስለመሰለኝ ነው! ታዲያላችሁ…የገንዘብ ፍቅራችን… አለ አይደል… “የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!” አይነት እየሆነ ወዳጅነት ሁሉ ዋናው ‘ክራይቴሪያ’ ጥቅም እየሆነ ነው፡፡ በአንድ ስኒ ሻይና በአንድ ያደረ ቦምቦሊኖ ከተማውን ሲያዞር የሚውል ወዳጅ… አለ አይደል… ‘ድሮ’ ቀርቷል፡፡ ጓደኝነት ማለት ምንቸት አብሽ በአንድ ጭልፋ ሁለትና ሦስት ቦታ አውጥቶ ተካፍሎ መብላት ነበር፡፡ ዘንድሮ ጓደኝነት ማለት የምንቸት አብሽ ስዕል ‘ሼር’ መደራረግ የሆነ ይመስላል… “ስሚ ሼር ያደረኩትን የምንቸት አብሽ ስዕል አየሻት!” አይነት ነገር ነው፡፡

(እንትና ስማኝማ…ምን የመሰለች በቅቤ ያበደች ሹሮ አለች፤ ፌስቡክ ገጽህ ላይ ፖስት አድርጌልለሁ…፡፡ ተዝናናባትማ!) ዘንድሮ በሰንበት ሙዝና ብርቱካን ይዞ ሄዶ የአክስትን ልጅ ‘ላይክ’ ከማድረግ ኮምፒዩተር ፊት ተቀምጦ የጄሎን ፌስቡክ ገጽ ‘ላይክ’ ማድረግ…የስልጣኔ ጣሪያን ‘ቀደን ለመውጣት ስለመድረሳችን’ ማሳያ ሆኗል፡፡ “ገንዘብ ቸግሮኝ ነው፣ አንድ መቶ ብር ታበድርኛለህ…” ብሎ ጥያቄ… አለ አይደል…ገና ኤንጂኦ ያልተቋቋመለት ጎጂ ልማድ ሆኗል፡፡ እናማ…“የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!” አይነት ነገር ምን ያህል እንደተጠናወተን የሚያሳብቅብን… ከሰማንያ ምናምን ሚሊዮን ሕዝብ መሀል ሦስት ሺህ የማይሞሉ ሚሊየነሮች አሉ ተብሎ… “መታሰቢያ ቀን ይሰየምላቸው…” አይነት ትርጉም ሊሰጡ የተቃረቡ ዘገባዎች ቀሺም ናቸው፡፡ አንዳንዴ ምን እላለሁ መሰላችሁ…ይሄ ሁሉ ማህበራዊ ችግር እያለ፣ በብዙ ነገር መንገድ ስተን እየሄድን እያለ ምነው እኛ የጨነቀንን ያህል ቦሶቻችንን ‘አይኮነስራቸውም’! ልክ ነዋ… “ምነው ሰዋችን ገረጣ…” ምናምን የሚሉ ሀሳቦች አይገባቸውምሳ! በዛ ሰሞን ከብዙ ዓመታት በኋላ ‘አገር ቤት’ ብቅ ያለች ‘ዳያስፖራ’ ምን አለችን መሰላችሁ…“ሰዉ ጠዋት ፊቱን ታጥቦ የሚያደርቀው በወፍጮ ቤት ጆንያ ነው እንዴ!” ይሄን ያህል ‘ነስንሶብናል’ ነው የምላችሁ! “የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!” ከሚል አይነት ገንዘብ ወዳድነት አንድዬ ይሰውረንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Page 10 of 16