አንድ የፈረንጆች ተረት አለ፡፡
ኮረዶች በማፍቀር ዕድሜ ላይ ያሉ ጐረምሶች፤ “የት ሄደን ነው ራት የምንገባበዘው?” ሲባባሉ፤ አንደኛው፤
“ኦሽን-ቪው ሆቴል እንሂድ” አለ
“ለምን?” ሲሉት፤
“እዚያ ቆንጆ ቆንጆ፣ የሚታዩ ኮረዶች አሉ!” አለ፡፡
ሁሉም ተስማሙና ሄደው በርቸስቸስ ሲሉና ሴት ሲያጫውቱ አመሹ፡፡
ይህ በሆነ ከአሥር ዓመት በኋላ እንደዚሁ ተገናኙ፡፡ “የት እናምሽ?” የሚል ጥያቄ ተነሳ!
“ኦሸን-ቪው ሆቴል” አለ አንዱ፡፡  
“ለምን?” አሉት፡፡
“ጥሩ ራትና ጥሩ መጠጥ አለ” አለ፡፡
ይህ በሆነ ከአሥር ዓመት በኋላ ዳግም ተገናኙ፡፡ አሁን ወደ ሰባ ዓመት ተጠግቷቸዋል እንግዲህ
“የት እንብላ ራት?” ተባለ፡፡
“ኦሺን ቪው ሆቴል” አለ አንደኛው፡፡
    *    *     *
“ለምን?” አሉት፡፡
“በጣም ፀጥ ያለ፣ የውቂያኖሱን ሰላምና ነፋሻ አየር የምናገኝበት ቦታ ነዋ!” አላቸው፡፡
ተያይዘው ነፋሻውንና ፀጥ ያለውን አየር ሲኮመኩሙ አመሹና ተለያዩ፡፡
ይሄ በሆነ ከአሥር ዓመት በኋላ እንደገና ተገናኙ፡፡ አሁን ጎብጠዋል፡፡ ከዘራ ይዘዋል፡፡ ባርኔጣ አድርገዋል፡፡ በጣም በዝግታ ነው የሚራመዱት፡፡ እየተደጋገፉ እየተቃቀፉ ነው የሚቆሙት፡፡
“ዛሬስ ለእራት የት እንሂድ?” አለ አንደኛው፡፡
“ኦሽን ቪው ሆቴል” አለ ሌላው፡፡
“ለምን?” ብለው ጠየቁ ሌሎቹ፡፡
ሰውዬውም፤
“እዛ ሆቴል ሄደን አናውቅማ!”
“ብራቮ! አዲስ ሆቴል ማየት በጣም ደስ ይላል” አለ አንዱ፡፡  
“ድንቅ ሀሳብ!”
“አስገራሚ ሀሳብ!”
“ጉደኛ ሀሳብ!” እየተባባሉ እየተጓተቱ፣ እየተገፋፉ፣ መሰሰሰስ እያሉ፤ ወደ ኦሽን ቪው ሆቴል አመሩ፡፡
*   *   *
የተፈጥሮን ሂደት ለማቆም አይቻልም፡፡ ይህን የተፈጥሮና የዕድሜ መሰላል፤ በየዕለቱ ከሚገጥመን አገራዊ ችግርና አፈታቱ ጋር ለማስተያየት ብንሞክር፤ አርጅተን ጃጅተን የሠራነውንና ያልሠራነውን፣ የሄድንበትንና ያልሄድንበትን ለመለየት የማንችልበት የመርሳት ዕድሜ እስከምንደርስ ንቅንቅ አልልም ብለን፤ በያዝነው ሥልጣንና ሹመት ሙጭጭ ካልን፤ በዚያውም ለተተኪው ትውልድ ቦታ ካልለቀቅን፤ የአገር- ለውጥ- ቀን እየራቀ ነው የሚሄደው፡፡ በእርግጥም ይሄ ቦታን በሰላም የመልቀቅ ባህል የዋዛ ነገር አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ-ገፅ አለው፡፡ የኢኮኖሚ-ገፅ አለው፡፡ የግል ጥቅም-ገፅ አለው፡፡ ከፓርቲ ጋር፣ከራስ ጥቅም ጋር፣ ከራስ ህሊና ጋር መሟገትንና መታገልን ይፈልጋል፡፡ ይህን ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ የሆነ በማይገኝበት ዘመን የአገር ምጧ ብዙ ነው፡፡
ወጣቱ ላይ ዕምነት ይኑረን፡፡ ያለ ጥርጥር ወጣቱ አሸናፊ ነው፡፡ The New is invincible ይሉ ነበር የጥንት ፖለቲከኞች፡፡ ዛሬም ይሄ ዕውነታ አይሻርም፡፡ አዲስ ኃይል መፍጠር የአገር አቅም መፍጠር ነው። ይህ ማለት ግን የግድ በፖለቲካ የሚታቀፍ ወጣት ይኑረን ማለት አይደለም፡፡
“ያፈረሰ ቄስ ተመልሶ አይቀድስ፣ የሸሸ ንጉሥ ተመልሶ አይነግሥ” በሚባልበት አገር የማይሻሩና በልብ ፅላት ላይ የተፃፉ ህግጋት አሉ፡፡ እነዚህ በባህልና በማህበራዊ ልምድ የዳበሩና የታመኑ ናቸው! አገር ያወቃቸውና ያመነባቸው የወል ህግጋት እንዳሉ ሁሉ፤ ሰው በግሉ በራሱ ላይ የሚወስንባቸው ግለ-ደንቦችም አሉ፡፡ እንዲህ ያሉት ህገ-ደንቦች ሲበራከቱ ስደት ልጓም ያጣል፡፡ ስደተኛው የትየለሌ ቢሆን የማይገርመው ለዚህ ነው! ውጤቱን እንደ ዛሬው በአስከፊ መልኩ ባንቀምሰውም በውሱን መልኩ የምናውቀው ስደትና አስከፊ ውጤት ነበር፡፡ “የራሱን ጭራ ሳያይ ውሻ ፍየልን ጭራሽን ዝቅ አድርጊ” ይላል የሚል ኦሮምኛ ተረት አለ፡፡ የራሳችን ነውር ሳይታየን ስለ ሌላው አስነዋሪ ነገር መናገር ክፉ እርግማን ነው! የሌሎቹን አገሮች፤ ፓርቲዎች፣ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ስንተች እኛስ? የእኛስ? ብለን መጠየቅን አንርሳ! ልማዶቻችንን፣ በዓሎቻችንን ስብሰባዎቻችንን እንገምግም፣ እንመርምር፣ እናሻሽል፡፡ በዓላት በራሳቸው ግቦች አይደሉም፡፡ ወደፊት መራመጃ እንጂ!  
ከፖለቲካ ባህላችን ውስጥ እጅግ ሚዛን የሚደፋ አንድ ባህል አለ፡፡ ብዙ ሊጤን ይገባል! የይቅር መባባል ባህል!  ቂም፣ የወንጀለኝነት-ስሜት፣ ብድር-የመመለስ ፍላጎት፤ አጥፊ ናቸው፡፡ ዴቪድ ሀውኪንስ እንዲህ ይለናል፡፡ “የ2ኛው የዓለም ጦርነት አንጋፋ ተሳታፊዎች አሰቃቂውንና አንገፍጋውፊን ጦርነት ከተወጡ በኋላ አብዛኞቹ የጠላት ተፋላሚዎች በፍጥነት ይቅርታ ተደራረጉ፣ ይቅር ተባባሉ፡፡ ሰላምታ ተሰጣጡ፡፡ የፍልሚያውን ፍፃሜም በዓል አከበሩ፡፡ በአዲስ የመተሳሰብ መንፈስ ተጨባበጡ፡፡ አሜሪካኖች አቶሚክ ቦምብ የጣሉና በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎችን የቀጠፉ ነበሩ፡፡ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ግን “በቃ ጦርነትኮ ይሄው ነው” ተባለ! የትላንት ተፋላሚዎች የዛሬ ጓደኛ ሆኑና ይጠያየቁ ጀመር፡፡ ይሄው እስካሁንም የተረፉት ታላቁን የጦርነት ቀን ያከብራሉ”
በአያሌ ሰዎች በተግባር እንደተረጋገጠው፤ አሉታዊ አመለካከትና የወንጀለኛነት ስሜት ፤በአዎንታዊ የመረዳት ስሜት፣ በመረዳዳትና በትውስታ ስሜት፤ ሊተካ ይችላል፡፡ … በዚህ ስሜት ሲታይ ከዚህ ቀደም ይጠሉ የነበሩ ሰዎች ይቅርታን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ያስፈሩ የነበሩ ሰዎችም አሁን ሰላማዊ ሆነው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ራስን ለማየትና ጥፋትን ለመቀበል ዝግጁ የመሆን ጉዳይ ነው። እርግጥ እንደኛ በፊውዳሊዝም ለተተበተበ፣ ባልለየለት ካፒታሊዝም ለታጠረና ሁሉን ጥፋት በሌሎች ላይ መላከክን ሥራዬ ብሎ ለያዘ ህብረተሰብ ፤ ከአባዜው በቀላሉ ለመገላገል አይቻልም! ሆኖም ይቻላል ብለን አዕምሮአችንንና ልቡናችንን ክፍት እናድርግ፡፡ ለዚህ ቁልፉ ነገር፤ አንዱ ከሌላው መማሩ ነው፡፡ ችግሩ ግን ያልተማረው የተማረውን ካላስተማርኩ፣ አላዋቂው አዋቂው ካላዳመጠኝ የሚልበት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአዕምሮም በአካልም ያልዳበረው ሰው፤ ልምድ ያለውንና የዳበረውን ሰው፤ ዘራፍ ሲልበት፣ ሲፎክርበት፣ ከእኔ ወዲያ ላሣር ሲለው የታየበት አገር መሆኑ ነው! “አውራ ዶሮ ፈረሱን ረግጦ፤ ‘እርግጫ ከእኔ ተማር!’” አለው፤ የሚለው የኦሮምኛ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው!!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አንዳንድ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ጉቦ እንድንሰጣቸው ሲደራደሩ ብዙ ንብረት ጠፍቷል - ተጐጂዎች ችግሩ በተነገረው መጠን አይደለም - እሳት አደጋ

             በመርካቶ የጅምላ መደብሮችና መጋዝኖች ላይ ረቡዕ ዕለት የተከሰተውን ቃጠሎ ለማጥፋት የተጠሩ የእሣት አደጋ መከላከያ ተቋም ሠራተኞች ጉቦ ጠይቀውናል በማለት ተጐጂዎቹ ለከተማዋ ከንቲባ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን፣ ተቋሙ አቤቱታውን በማስተባበል ሦስት ሰራተኞች እንደቆሰሉበት ገለፀ፡፡ ለ5 ሰዓታት የዘለቀው ቃጠሎ፤ ከ40 በላይ መደብሮችና መጋዘኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱም በተጨማሪ ከ30 በላይ ሰዎችም እንደተጐዱ ተገልጿል፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ በስፍራው ተገኝተው ተጐጂዎችን ያነጋገሩ ሲሆን፣ በእሣት አደጋ መከላከያ ተቋም ሠራተኞች ላይ አቤቱታ አሰምተዋል። የተቋሙ ሰራተኞች በቦታው ከደረሱ በኋላ፣ “እሳቱን ለማጥፋት ከበላይ አካል መመሪያ አልተላለፈልንም” በሚል ሰበብ “ቆመው ሲያዩ ነበር” በማለት ምሬታቸውን የገለፁ ተጎጂዎች፤ አንዳንድ የተቋሙ ሰራተኞች ደግሞ “ጉቦ እንድንሰጣቸው ሲደራደሩ ብዙ ንብረት ጠፍቷል” ብለዋል፡፡ መጋዘንና መደብር እንደወደመባቸው ለአዲስ አድማስ የገለፁ ነጋዴ፤ እሣት አደጋዎች የድረሱልን ጥሪው ከተላለፈላቸው በኋላ ዘግይተው ነው የመጡት፤ እዚህ ከደረሱ በኋላም መመሪያ አልተላለፈልንም በሚል ቆመው ይመለከቱ ነበር ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በአካባቢው ከ4 ጊዜ በላይ የእሣት አደጋ መድረሡንና የአሁኑ ቃጠሎ ከሁሉም የከፋ መሆኑን የተናገሩ ሌላ ነጋዴ በበኩላቸው፤ የአካባቢው ሰው እሳቱን ለማጥፋት ሲረባረብ የእሣት አደጋ ሠራተኞች ከበላይ ትእዛዝ እየጠበቅን ነው በማለት ቆመው መመልከታቸው እንዳሣዘናቸው ገልፀዋል፡፡ “ከዚህ ቀደም በፍጥነት እሳት ለማጥፋት ክሬን ይጠቀሙ ነበር፤ አሁን ለምን ክሬን እንዳልተጠቀሙ እንዲገለፅልን እንፈልጋለን” የሚሉት እኚሁ ቅሬታ አቅራቢ፤ የወገን ንብረት እየወደመ መመሪያ እንጠብቃለን ብሎ መቆም አሣዛኝ ነው ብለዋል፡፡ ከንቲባ ድሪባ ኩማ፤ የተጐጂዎቹን አቤቱታ ካዳመጡ በኋላ “መመሪያ አልተላለፈልንም ወይም ገንዘብ ክፈሉኝ” ብሎ ዳተኝነት ያሳየ ሰራተኛ ካለ፣ ራሴ የማጣራው ጉዳይ ነው፣ የአደጋው መንስኤም በቶሎ ተጣርቶ ይገለጻል” ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ እሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ በበኩላቸው፤ የአደጋውን የጥፋት መጠን በገንዘብ ለማስላት ለጊዜው ባይቻልም 40 የንግድ ሱቆች እና 5 መጋዘኖች ከነሙሉ ንብረታቸው መውደሙን ተናግረዋል፡፡

32 ሰዎች ቀላል ጉዳት እንደደሠረባቸውና ከነዚህ መካከል ሶስቱ የእሣት አደጋ ባለሙያዎች ሲሆኑ በጦር ሃይሎች ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ነው ብለዋል-አቶ ንጋቱ፡፡ እሣቱን ለማጥፋት አስፈላጊው መስዋዕትነት ተከፍሏል ያሉት አቶ ንጋቱ፤ “ጉዳት የደረሠበት ሠው ቅሬታ ለምን አቀረብክ ባይባልም፤ ባለሙያዎቹ በቸልታ ይመለከቱ ነበር፣ በገንዘብ ይደራደሩ ነበር የሚለው አባባል ስሜታዊነት የተንፀባረቀበት ነው፤ ችግሩ በተነገረው መጠን አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሠጥተዋል፡፡ በፍጥነት ባለሙያዎች አልደረሡም ለተባለውም በትራንስፖርት መጨናነቅ ምክንያት 10 ደቂቃ ያህል ብቻ መዘግየት ማጋጠሙን የተናገሩት አቶ ንጋቱ፤ ቦታው አመቺ ባለመሆኑ፣ ተቀጣጣይ ነገሮች በብዛት በመኖራቸው፣ በአቅራቢያው ውሃ ባለመኖሩ እና ስራውን ለባለሙያዎች ያለመተው ችግር ተደማምረው በሚፈለገው ፍጥነት እሣቱን መቆጣጠር አልተቻለም ብለዋል፡፡ እሣቱን ለማጥፋትም 10 የአደጋ መከላከያ መኪኖችና 7 አምቡላንሶችን በመጠቀም 585 ሺህ ሊትር ውሃ እና 144 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ድርጅታቸው መጠቀሙን የገለፁት ሃላፊው፤ ክሬን መምጣት ነበረበት ለተባለው ድርጅቱ ያሉት ክሬኖች ለዚህ ጉዳይ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አይደሉም ብለዋል፡፡

Published in ዜና

“አገራችን ታላቅ ልጇን አጥታለች፣ ህዝባችን አባቱን ተነጥቋል፣ ይህቺ ቀን መምጣቷ እንደማይቀር ብናውቅም የዛሬዋ እለት ይዛው የመጣችው ሃዘን ፍጹም ጥልቅና በምንም ነገር የማይሽር ነው!!” የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮቭ ዙማ፣ ጥቁር ለብሰው በአገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አሉና መሪር ሃዘን ባጠላበት ፊት፣ በተሰበረ አንደበት ተናገሩ፡፡ ይህ ደቡብ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን መላውን አለም ያስደነገጠ፣ የብዙዎችን ልብ ክፉኛ የሰበረ ትልቅ መርዶ ነው - ብሄራዊ ሃዘን፡፡ ከትናንት በስቲያ እኩለ ሌሊት ገደማ አለም የማዲባን መፈጸም ተረዳ፡፡ የጸረ አፓርታይድ ታጋዩ፣ የመብት ተሟጋቹ፣ የነጻነት ተምሳሌቱ፣ የይቅርታ ምልክቱ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ሮሊህላላ ማንዴላ በተወለዱ በ95 አመታቸው ሃሙስ ሌሊት ተፈጸሙ፡፡ ትራንስኪ ላይ የጀመረው የማንዴላ የህይወት ጉዞ፣ ዘመናትን ከዘለቀ የትግል፣ የፈተና፣ የድል… የክፉና የደግ፣ የዳገትና የቁልቁለት ፍሰት በኋላ፣ ከትናንት በስቲያ ጆሃንስበርግ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተቋጨ፡፡ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ ጤና ከራቃቸው አመታት ተቆጥረዋል። የጤናቸው ጉዳይ አልሆን ብሏቸው ከአደባባይ የራቁትና ቤት መዋል የጀመሩት እ.ኤ.አ በ2004 የመጀመሪያዎቹ ወራት ገደማ ነበር፡፡ ጤና ውሎ ማደር ያቃታቸው ማንዴላ፣ ከዚህ በኋላ ያሉትን አመታት በቤታቸውና በሆስፒታሎች መካከል እየተመላለሱ ነው ያሳለፉት፡፡ የጤናቸው ጉዳይ እየዋል እያደር አሳሳቢ መሆኑን የቀጠለው ማንዴላ፣ እስካለፈው መስከረም የነበሩትን ሶስት ወራት ፕሪቶሪያ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው ክፉኛ የጸናባቸውን የሳንባ ኢንፌክሽን በመታከም ነበር ያሳለፉት፡፡ ህክምናው ተስፋ እማይሰጥ መሆኑ ታውቆ በመስከረም ወር መጀመሪያ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንዲመለሱ የተደረጉት ማንዴላ፣ ዙሪያቸውን በቤተሰቦቻቸው ተከበው በተኙበት ነው ሃሙስ ምሽት ይህቺን አለም የተሰናበቱት፡፡ የማዲባን ህልፈት በውድቅት ሌሊት የሰሙት ደቡብ አፍሪካውያን፣ በእንቅልፍም ሆነ በእረፍት የሚያሳልፉት ቀሪ ሌሊት አልነበራቸውም፡፡ መሪር ሃዘን ልባቸውን የሰበረው ደቡብ አፍሪካውያን ስለ ማንዴላ እንባቸውን አፈሰሱ፡፡ ከሶዌቶ እስከ ፕሪቶሪያ፣ ከኬፕታውን እስከ ጆሃንስበርግ በመላ አገሪቱ ሃዘን ሆነ፡፡ “ማዲባ!... ማዲባ!... ማዲባ!...” ሁሉም ይህን ስም መጥራት፣ ይህን ሰው ማሰብ ያዘ፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ስለ ጀግናቸው ሻማ ለኩሰው አደባባይ ወጡ፡፡ በጥቁሩ ጨለማ ውስጥ ‘የጥቁሩን ብርሃን’ ፎቶግራፎች ይዘው ጎዳናዎችን ሞሏቸው፡፡ “ማንዴላን አላየነውም የታሰረበት ሄደን ማንዴላን አላየነውም!...” እያሉ የክፉ ቀን ዜማቸውን አቀነቀኑ፡፡ የአፓርታይድ አገዛዝ ዘመን መዝሙሮችን ከፍ ባለ ድምጽ ዘመሩ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሰንደቅ ዓላማ፣ በትግልና በመስዋዕትነት ከፍ ላደረጓት የአርነት ታጋዩዋ ዝቅ ብላ ተውለበለበች፡፡ ሀዘኑ የደቡብ አፍሪካውያን ብቻ አይደለም፡፡ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከጃኮቭ ዙማ አንደበት የተሰማውን መርዶ እየተቀባበሉ አስተጋቡት። የአለም ህዝቦች በሰሙት ነገር ክፉኛ ደነገጡ፣ አብዝተው አዘኑ፡፡ “እሳቸው የሰሩት፣ ከማንኛውም ሰው ከሚጠበቀው በላይ ነው፡፡ ስራቸውን ፈጽመው ወደማይቀረው ቤታቸው ቢሄዱም፣ ማንዴላ የዘመናት ሁሉ ሃብት ናቸው” አሉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ ከወደ ኋይት ሃውስ ባሰሙት የሃዘን መግለጫ ንግግራቸው፡፡ በሞታቸው ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው በስሜት ተውጠው የተናገሩት ኦባማ፤ የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማዎች በሙሉ እስከ ሰኞ ድረስ ስለማንዴላ ክብር ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ የአሜሪካም ብቻ ሳይሆን የፈረንሳይና ሌሎች አውሮፓ አገራት፣ የአውሮፓ ህብረት እና የፊፋ ባንዲራዎችም ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ ተወስኗል፡፡ ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከእስያ እስከ መካከለኛው ምስራቅ በአለም ዙሪያ ያሉ የሌሎች በርካታ መንግስታትም ስለ ማንዴላ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን መግለጽ ይዘዋል፡፡ “እጅግ እጅግ አዝኛለሁ! ለአገሩ በጎ ነገር ለማምጣት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሲሰራ የኖረ ታላቅ ሰው ነው፡፡ የማንዴላን ታላቅነት የምትመሰክረው፣ ሰላም ውላ የምታድረው ደቡብ አፍሪካ ናት!” ብለዋል የእንግሊዟ ንግስት ኤልዛቤጥ መርዶውን እንደሰሙ ከቤኪንግሃም ቤተመንግስት ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ መልዕክት፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን በበኩላቸው፣ “ለፍትህ የተጋ ታላቅ ሰው፣ ለሰው ልጆች የበጎነት ምሳሌና የመነቃቃት ምንጭ” በማለት ነው ማንዴላን የሚገልጹዋቸው፡፡ “በታሪካችን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ተገኝቶ ይመራን ዘንድ ማንዴላን የፈጠረልን አምላክ፣ እኛን ደቡብ አፍሪካውያንን አብዝቶ ይወደናል” ያሉት ደግሞ ታዋቂው ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ናቸው፡፡ ከነገ በስቲያ ሰኞ ጆሃንስበርግ ውስጥ በሚገኘውና 90 ሺህ ሰው በሚይዘው ኤፍ ኤን ቢ ስቴዲየም በሚከናወን ብሃራዊ የሃዘን ስነስርዓት በድምቀት የሚዘከሩት ማንዴላ አስከሬን፣ ለሶስት ቀናት ያህል በመዲናዋ ፕሪቶሪያ በህዝብ ሲታይ ይቆያል፡፡ በመጪው ሳምንት መጨረሻም በብሄራዊ ክብር ታጅቦ በምስራቃዊ ኬፕታውን አቅራቢያ በምትገኘው የዕድገት መንደራቸው ኮኑ ወደሚማስለት መቃብር ይሸኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

Published in ዜና

በርካታ ድርጅቶች በሽብር ላይ የሚያተኩር መጽሐፋቸውን በተጽዕኖ እንዲገዟቸው አድርገዋል

ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና ሃብት አፍርተዋል የቀድሞው የደህንነት አባልና የትግራይ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል፤ ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን ፈጽመውታል በተባለው የሙስና ወንጀል ተጨማሪ 11 ክስ ቀረበባቸው፡፡ ግለሰቡ ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋርም በሌላ መዝገብ መከሰሳቸው ይታወሣል፡፡ አቶ ወልደስላሴ፤ አሁን ለተጨማሪ ክስ የዳረጋቸውን ወንጀል ፈፀሙ የተባለው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መ/ቤት ሠራተኛ በነበሩበት ጊዜ ሲሆን ከፊሉን ከወንድማቸው አቶ ዘርአይ ወ/ሚካኤል፣ ከእህታቸው ወ/ሮ ትርሃስ ወ/ሚካኤል እንዲሁም ከቅርብ ጓደኛቸው አቶ ዳሪ ከበደ ጋር በመመሳጠር፣ ከፊሉን ለብቻው እንደፈፀሙ ተገልጿል፡፡ ከትናንት በስቲያ ክሣቸው በንባብ የተሰማው አቶ ወልደስላሴ፤ በ1ኛነት የቀረበባቸው ክስ፤ የደህንነት መስሪያ ቤት ባልደረባ መሆናቸውን መከታ በማድረግ፣ በ2002 ዓ.ም “Terrorism in Ethiopia and the Horn of Africa” የተሰኘ መጽሐፋቸውን፣

ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገ/ስላሴ ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት በመጠቀምና ግለሰቡን በማታለል፣ ኤጀንሲው በሚያስተዳድራቸው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት፣ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት እና አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት ስፖንሰር አድራጊነት፣ 3ሺህ መጽሐፍት በ124,000 ብር እንዲታተሙ አስደርገው በመሸጥ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ይላል፡፡ በዚያው ክስ ላይ በ2ኛነት የቀረበው ክስ ደግሞ፤ ግለሰቡ በዚያው አመት ይህንኑ መጽሐፍ 10ሺህ ኮፒ ለማሳተም በሚል የመጽሐፉ ይዘት ከቴሌኮሙኒኬሽን ጋር ባልተገናኘበት እና የማስተዋወቅ ስራም ባልተሠራበት ሁኔታ የደህንነት አባልነታቸውን መከታ በማድረግ ከወቅቱ የቴሌኮምኒኬሽን ሃላፊ አቶ አማረ አምሣሉ ከ385ሺ ብር በላይ መቀበላቸውን ይጠቁማል፡፡

በዚሁ ክስ ላይ በ3ኛ እና በ4ኛነት በቀረቡት ክሶች፤ ግለሰቡ በኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ አክሲዮን ማህበር እንዲሁም በሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ የነበራቸውን የቦርድ አባልነት እንዲሁም የደህንነት ሠራተኛነታቸውን መከታ በማድረግ፣ የአክሲዮን ማህበራቱ 310 መጽሐፍትን በ62ሺ ብር እንዲገዙ ካስደረጉ በኋላ፤ ገንዘቡንም መጽሐፍቱንም ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ተጠቅሷል፡፡ በመዝገቡ በ2ኛነት የቀረበውም ክስ ደግሞ ግለሰቡ የደህንነት ሠራተኛ መሆናቸው የፈጠረላቸውን ተሠሚነት እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ፣ ወደ 26 የሚሆኑ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች የተለያየ ብዛት ያላቸውን መጽሐፍት እንዲገዙ ካስደረጉ በኋላ፣ መጽሐፍቶቹን ሳያስረክቡ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ይላል፡፡ ከእነዚህ መካከል የአልሣም ኃላ.የተ.የግ ማህበር ባለቤት አቶ ሣቢር አረጋው፤ ያለፍላጐታቸው በሌላ መዝገብ ክስ በቀረበባቸው በአቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ እና በባለሀብቱ በአቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር በኩል 500 መጽሐፍትን በመቶ ሺህ ብር እንዲገዙ ካስደረጉ በኋላ መጽሐፍቱን ለግላቸው አስቀርተው መጠቀማቸው፣ ጌታስ ትሬዲንግ 1500 መጽሐፍትን፣ ነፃ ፒኤልሲ 700፣ ካንትሪ ትሬዲንግ 300፣ ሐበሻ ካፒታል ሠርቪስ 50፣ አኪር ኮንስትራክሽን 100 መጽሐፍትን እንዲሁም በርካታ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተለያየ ብዛት ያላቸውን መጽሐፍት እንዲገዙ ካደረጉ በኋላ፣ መጽሐፍቶቹን ሳያስረክቡ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ተመልክቷል፡፡

በግለሰቡ ላይ በ3ኛነት በቀረበው ክስ፣ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ያለአግባብ በመጠቀም በመዝገቡ ስሟ የተጠቀሰን ግለሰብ በመንግስት መኪና ቁልቢ ድረስ እንድትሄድና በተለያየ ጊዜ እንድትዝናና አስደርገዋል እንዲሁም ግለሰቧ ለነበረባት የፍትሃብሔር ክርክር የመ/ቤቱን ሠራተኛ መድበው፣ መደበኛ ስራውን ትቶ እንዲከታተል አስደርገዋል ይላል፡፡ በ4ኛ እና በ5ኛነት የቀረቡባቸው ክሶችም፤ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ፣ አቶ ሣቢር አርጋው የተባሉት ባለሃብት ጋ በመደወል፣ ለሚሠሩት ቤት ሴራሚክ እንደጐደላቸው በመንገር፣ ግለሰቡ በ65ሺህ ብር እንዲገዙላቸው ማስደረጋቸው እንዲሁም ከመጽሐፍቶቹ ሽያጭ መንግስት ይፈልገው የነበረውን ከ496ሺህ ብር በላይ ግብር አሳውቀው አለመክፈላቸው በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ላይ ቀርቧል፡፡ ቀሪዎቹ ክሶች ከቤተሰብ አባላቱ ጋር ተጣምረው የቀረቡ ሲሆን በመዝገቡ ከ6ኛ እስከ 9ኛ ክስ ሆኖ የቀረበው፣ አቶ ወልደስላሴ፤ 2ኛ ተከሣሽ የሆኑትን ወንድማቸው አቶ ዘርአይን የመኖሪያ ቤታቸው ወኪል በማድረግ፣ ቤቱ ከመኖሪያ ቤት ውጪ ለሆነ አገልግሎት እንዲውል ካደረጉ በኋላ፣ መንግስት ይፈልገው የነበረውን ከ126ሺ ብር በላይ ግብር በተገቢው መንገድ አሳውቀው አልከፈሉም፤ በዚህም የሃሰት ወይም አሳሳች መረጃ በማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል ይላል፡፡ በተጨማሪም ከ119ሺ ብር በላይ የተርን ኦቨር ታክስ ግብርም አልከፈሉም ተብሏል፡፡

በሁሉም ላይ የቀረቡት ቀሪዎቹ ክሶች ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ይዞ መገኘት የሚሉ ናቸው፡፡ 1ኛ ተከሣሽ ለወንድም እና እህቶቹ እንዲሁም ለቅርብ ጓደኛው ውክልና እየሰጡና ንብረትን በማስተላለፍ ዘዴ እየተጠቀሙ ሃብት አፍርተዋል ይላል፡፡ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ተብለው ከተጠቀሱት መካከልም በአቶ ወልደስላሴ እና በባለቤታቸው ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምስት የተለያዩ ቅርንጫፎች ከ9ሺ እስከ 1 ሚሊዮን 5 መቶ ሺ ብር በማስቀመጥና በማንቀሳቀስ ሲጠቀሙ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ይህ ሲሆን የግለሰቡ ደሞዝ ከ1600 እስከ 6ሺህ ብር ነበር ብሏል አቃቤ ህግ፤ ሁለተኛ ተከሣሽ ደግሞ በመከላከያ ውስጥ ተቀጥሮ ሲሠራ ደሞዙ 523 ብር ሆኖ ሳለ፣ በ3 የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ከ150 ሺ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ሲያንቀሳቀስ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ምንም የገቢ ምንጭ እንደሌላት የተገለፀው እህቱ እና ጓደኛውም በውክልና እና በማስተላለፍ ሂደቶች የእርሻ ልማት ኢንቨስትመንት እና በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ እና በአክሱም ቦታ እና ቤት፣ እንዲሁም በባንክ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ አስቀምጠው መገኘታቸው በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በእለቱ ክሣቸውን ፍ/ቤቱ በንባብ ካሠማ በኋላ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሣሽ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ የአቃቤ ህግን መልስ መነሻ በማድረግ ውድቅ ካደረገ በኋላ፣ ተከሣሾች የሚያቀርቡትን መቃወሚያ ወይም መከራከሪያ ለመጠባበቅ መዝገቡን ለታህሣስ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

Published in ዜና

ህገወጥ ናችሁ ተብለው ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያዊያን፤ ለበርካታ አመታት ለፍተን ያፈራነውን ንብረት ይዛችሁ መግባት አትችሉም ተብሎ ተነጥቀናል፡፡ የፍተሻ ሰራተኞች ሻንጣዎቻቸውን በመፈተሽ፣ ሞባይል ከአንድ በላይ ከያዙ ትርፉን በማስቀረት፣ አዳዲስ አልባሳት እና ኤሌክትሮኒክስ ቁሰቁሶች የተወሰኑትን ብቻ በመፍቀድ እና ያመጡትን ወርቆች ግራም በመቀነስ ንብረታቸውን እየወሰዱባቸው እንደሆነ ተመላሾቹ ገልፀዋል፡፡ መሃመድ አባመጫ የተባለ የሳኡዲ ተመላሽ፤ ከሳውዲ ስድስት ሻንጣ ይዞ መምጣቱን ገልፆ፤ ቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ ሲደርስ ግን ከሁለት ሻንጣ በላይ ይዞ መግባት እንደማይችል፣ ከአምስት ሞባይሎችም ሁለቱ ብቻ እነደተፈቀደለት ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ የሳውዲ መንግስት ከአንድ ኪሎ በላይ ወርቅ ይዛችሁ መውጣት አትችሉም የሚል መመሪያ ማሳለፉን የጠቆመው ተመላሹ፤ ንብረቱን እዚያው ጥሎ ለመመለስ መገደዱን ገልጿል፡፡ የሳኡዲ መንግስት እንኳን ከወርቅ በስተቀር ሌላ ንብረታቸውን ሁሉ ይዘው እንዲወጡ መፍቀዱን የገለፀው መሃመድ፤ በአገራቸው ንብረታቸውን እንዳያስገቡ መከልከላቸው እንዳሳዘነው ይናገራል፡፡

ኤሌክትሮኒክስና ለቤተሰቦቹ ያመጣውን ልብሶች ቀረጥ ከፍለህ ነው የምትወስደው በመባሉ፣ ለሁለት ቀን በስደት ተመላሾች በተዘጋጀው ድንኳን ውስጥ ያለምንም ፍራሽና ልብስ ተኝቶ ንብረቱን ቢጠብቅም ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል፡፡ “ሳዑዲም እዚህም ሀገራችን ስንደርስ እየበደሉን ያሉት ሃበሾች ናቸው” ያለው መሃመድ፤ መንግስት በሚዲያ በተሟላና በተደላደለ መንገድ እንደሚቀበለን ቢገልፅም እዚህ የጠበቀን ግን ሌላ ነው ሲል ቅሬታውን ገልፆ “ሌላው ቢቀር እስካሁን ተመላሾቹን የሚያመላልሰው እንኳን የሳዑዲ እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት አይደለም” ብሏል፡፡ ከሳኡዲ ካመጣችው ወርቅ ላይ ሃምሳ ግራሙን ብቻ እንደምትወስድ የተነገራት ተኪያ ሙሃመድን ያገኘናት በቁጭት መሬት ላይ እየተንከባለለች ነበር፡፡

ተኪያ እያለቀሰች እንደነገረችን፤ ለ14 ዓመት ሰርታ ከሶስት መቶ ሃምሳ ግራም በላይ ወርቅ እንዳጠራቀመች ገልፃ፤ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከሳውዲ እንድትወጣ ከመገደዷ በፊት ሙሉ ንብረቷን አስቀድማ ብትልክም እስካሁን እንዳልደረሰላት ትናገራለች፡፡ አሁንም፤ ከተመለሰች በኋላ የያዘቻቸውን ሻንጣዎች ለመውሰድ እንዳልቻለች የምትገልፀው ተኪያ፤ በፍተሻ ስም ሰራተኞቹ ሻንጣዋን በርብረው በማየት፣ ያመጣቻቸውን የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችና ሶስት ሞባይሎች መውሰዳቸው ሳይንስ፣ ሶስት መቶ ግራም የሚመዝን የወርቅ ንብረቷን እንዳታስገባ መከልከሏን በጩኸት ትናገራለች፡፡ ለምን ንብረቷን እንደከለከሏት ስትጠይቅም “እናንተ ነጋዴዎች ናችሁ፤ በስደተኞች ስም ያለቀረጥ ንብረት ለማስገባት ትፈልጋላችሁ” በማለት ሰራተኞቹ እንደመለሱላት ገልፃ፤ ጉዳዩን ለአለቆቻቸው ለማመልከት ብትፈልግም የሚያናግራት ሰው አለማግኘቷን ጠቁማለች፡፡ በዚሁ ስፍራ ያገኘናቸው በርካታ ተመላሾች፤ የንብረታቸው ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ። ንብረታቸውን ሳይዙ ወደቤተሰቦቻቸው ላለመቀላቀል በሚል የተሰበሰቡበት ካምፕ፣ ምንም ለማረፊያ የተመቻቸ አገልግሎት ባለመኖሩ መቸገራቸውንም ገልፀዋል፡፡ መንግስት የሚሰጣቸውን 900 ብር፣ በትራንስፖርትና በስልክ አገልግሎት እንደሚጨርሱ አክለው ተናግረዋል፡፡

በርካቶች በእቃዎቻቸው መታገድ በመበሳጨታቸው ጭቅጭቅና አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ ለመግባት መገደዳቸውን ተመላሾቹ ይናገራሉ፡፡ “ስንመጣ የሚሰጠንን ሊሴ ፓሴን አይተው ማስተናገድ ሲገባቸው እነሱ ግን ንብረታችንን እየወሰዱብን ነው” በማለት የሚናገሩት ተመላሽ ዜጎቹ፤ “ምናልባትም ንብረት የላቸውም ብለው አስበውን ይሆናል፤ ነገር ግን በርካታ አመታት ስንቆይ መቼም ባዶ እጃችንን አንመጣም” በማለት በምሬት ይናገራሉ፡፡ “ዛሬ እቃችንን የከለከሉን ነገ ምን ተስፋ ይዘን ነው ተደራጅታችሁ ስራ ስሩ ለሚሉን?” የሚሉት እነዚህ ተመላሾች፤ “በመንግስት ላይ አመኔታ የጣልነው ሳውዲ ድረስ በተወካዮቹ አማካኝነት መጥቶ ባናገረን መሰረት ነበር፤ ነገር ግን የተገባልን ቃል ታጥፏል” ይላሉ፡፡ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠቱ እና ለቤተሰብ መርዶ ባለመነገሩ፣ ለሚያውቋቸው ቤተሰቦች መርዶ ለመንገር ጭንቀት ላይ መሆናቸው ሌላ ችግራቸው እንደሆነ የተናገሩት ተመላሾች፤ አሁንም ቢሆን ሳውዲ ላይ ሃበሻዎችን በመኪና እየገጩ መግደል የሳውዲ ፖሊሶች የቀን ተቀን ስራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ታዲያ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ አምልጠው የሚመለሱ ዜጐችን ንብረት መቀማት ምን የሚሉት ተግባር እንደሆነ አልገባንም፤ በማለት አማርረዋል-ተመላሾቹ፡፡ ምናልባትም የፖለቲካ ማራመጃ ሊያደርጉን ነው በማለትም ስጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

ተመላሾቹ የተሟላ መጠለያ ተዘጋጅቶላችኋል በተባለበት ቦታ ሳይቀር፣ መተኛ ሥፍራ እንኳን እንዳልተዘጋጀ ሲረዱ ተስፋ መቁረጣቸውን እና ንብረታቸውን እንዳያስገቡ ሲከለከሉ፣ ተመልሰው በህገወጥ መንገድ ለመሰደድ ሙከራ መጀመራቸውን ይገልፃሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፤ “ተመላሾቹ ስለንብረት የሚያነሱትን ጥያቄን በተመለከተ፤ እኛ ተመላሾች በሙሉ ንብረት እንደሌላቸው ነው የምናውቀው“ በማለት ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ አልፎ አልፎ ባዶ እግራቸውን ከሳዑዲ የተመለሱ እንዳሉ ጠቁመው፤ በሳኡዲ መንግስት ጓዛችሁን ይዛችሁ እንዳትወጡ ተከልክላችኋል በመባላቸው፣ መጀመሪያውኑም ንብረት ይዘው ባለመምጣታቸው ነው፤ ብለዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች ከመደበኛ የአየር መንገዱ ተጓዦች እኩል እንደማይስተናገዱና ለብቻቸው ተጠብቀው እንደሚስተናገዱ ገልፀው፤ ምናልባት ከነዚህ ዜጎች ጋር ተቀላቅለው የሚመጡ ሌሎች ሰዎች ስለሚኖሩ እሱን ለማጣራት ንብረታቸው ይፈተሻል እንጂ ማንም የእነሱን ንብረት የሚወስድ እንደሌለ የተናገሩት አምባሳደሩ፤ እንኳን በሀገር ውስጥ የገባ ንብረት፣ ሳዑዲ ያለውንም የላባቸውን ውጤት ለማስመጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የሟቾችን ቁጥር እና ለቤተሰቦቻቸው መርዶ አለመንገርን በተመለከተ አምባሳደሩ በሰጡት ምላሽ፣ አሁን ሙሉ በሙሉ ትኩረታችን በህይወት ያሉ፣ ንብረታቸውን ያጡ እና ጉዳት የደረሰባቸው ላይ ነው፤ ብለዋል፡፡ የሟቾቹን ቁጥር በተመለከተ ግን መንግስት ከገለፀው በኋላ፣ የተፈጠሩ ነገሮች መኖራቸውን አምነው፤ ነገር ግን ቁጥሩ ላይ ተመላሾች የሚሉትና አንዳንድ ሚዲያዎች የሚያወሩት ትክክል ሊሆን ቢችልም የተጣራ ነገር እስካላገኘን ድረስ የሞቱበትን ሁኔታ ለማወቅ ያስቸግራል፤ ብለዋል፡፡ የሳውዲ አየር መንገድ እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመመለሱ ሂደት ምንም አስተዋፅአ ለስደተኞቹ አላደረገም ለተባለው አምባሳደሩ መልስ ሲሰጡ፡- የሳውዲ አውሮፕላን የሚያመላልሰው እራሱ በማባረሩ ምክንያት ነው፤ ወጪውን የሚችለውም እራሱ ነው ብለዋል፡፡

Published in ዜና

በኢትዮጵያ የብሪጅስቶን ጎማ ብቸኛ አስመጪና አከፋፋይ ካቤ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ በአዲስ አበባ ቃሊቲ መናኸሪያ አካባቢ ያስገነባው ‘ብሪጅስቶን ትራክ ታየር ሴንተር’ (BTTC) የተሰኘ አዲስ የጎማ ጥገና ማዕከል ትናንት ተመርቆ ተከፈተ፡፡ ላለፉት አስራ ሶስት አመታት ጥራታቸውን የጠበቁ የብሪጅስቶን ጎማዎችን በማስመጣት የሚታወቀው ካቤ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፤ በአገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንዳለ ይታወቃል፡፡ አገራት በሚጠቀሙበት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ዘርፈ ብዙ የተሽከርካሪ ጎማ ጥገናና ተያያዥ አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ ማዕከሉን እንደገነባ የብሪጅስቶን ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሁሴን አህመድ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

ደንበኞች የተለያዩ አገልግሎቶችን በምቹ ሁኔታ በሚያገኙበት መልኩ በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባውና በዘመናዊ ቁሳቁስ የተደራጀው ማዕከሉ፣ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸውን የጎማ ምርቶች ከማቅረቡ በተጨማሪ፣ የካበተ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች አማካይነት ሰባት አይነት የተለያዩ የተሽከርካሪ ጎማ ጥገናና ተያያዥ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ ማዕከሉ ከዚህ በተጨማሪም፤ ከጎማ አጠቃቀም፣ ከአጠቃላይ የተሽከርካሪዎች ደህንነት አጠባበቅና ጥገና ጋር በተያያዘ ለአሽከርካሪዎችና ባለሃብቶች የተሟላ መረጃና ሙያዊ ምክር ይሰጥበታል ተብሏል። ካቤ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በጥናት ላይ ተመስርቶ ባቋቋመው በዚህ ማዕከል ሊሰጣቸው ያቀዳቸው በቴክኖሎጂ የታገዙና የተሻሻሉ አገልግሎቶች፣ የተሽከርካሪዎችንና የጎማዎችን ዕድሜ ከማራዘም ባለፈ ለአዳዲስ ጎማዎች ግዢ፣ ለጥገናና ለእድሳት የሚወጣውን ወጪ በመቀነስ ረገድም የጎላ ሚና እንደሚጫወት በማዕከሉ ምረቃ ላይ ተነግሯል።

ከካቤ ሃላፊነቱ የተወሰነ የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ ከአቶ ሰኢድ አል አሙዲ ጋር በመሆን ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት የዕለቱ የክብር እንግዳና የብሪጅስቶን ኩባንያ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ፕሬዚዳንት ሚስተር ሳኩማ በበኩላቸው፤ የማዕከሉ መገንባት ለተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው ለወደፊትም ከካቤ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር ያለውን የስራ ግንኙነት በማጠናከር፣ የተሻሻሉ አሰራሮችንና ጥራታቸውን የጠበቁ የጎማ ምርቶችን ለደንበኞች ማቅረቡን እንደሚቀጥልበትም ሚስተር ሳኩማ ገልጸዋል፡፡ ካቤ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ከብሪጅስቶን ጎማ አስመጪነት በተጨማሪ በቡና ኤክስፖርት፣ በሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች አስመጪነትና በሳኡዲ ኤርላይንስ ብቸኛ ወኪልነት ሰፋፊ የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡

Published in ዜና

በገቢ ማሰባሰቢያ 20ሚ. ብር ይጠበቃል

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተመሰረተበት 1913 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ደርግ ውድቀት 1983 ዓ.ም ድረስ ያለውን የሰባ አመት ታሪክ የሚዘክር መጽሐፍ ሊታተም ነው፡፡ ለመጽሐፉ ማሳተሚያና የአየር ኃይል ቬንተራንስ አሶሴሽንን ለማጠናከር በሸራተን አዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ታህሳስ 24 ቀን 2006 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ የአየር ኃይል ቬንተራንስ አሶሴሽን አመራር አባላት ሰሞኑን በድሪም ላይነር ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ የአየር ኃይሉን የሰባ አመት ታሪክ ለመፃፍ ረጅም ጊዜ የወሰደባቸው ሲሆን ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የተገኙ መረጃዎችንና ቀደምት ፎቶግራፎችን በመጽሐፉ ለማካተት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡

መጽሐፉ የተፃፈው ከደርግ ውድቀት በፊት በአየር ኃይሉ ይሰሩ በነበሩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ሲሆን መጽሐፉን ለመፃፍ የሚያስችል መረጃ ለማሰባሰብ በሚደረገው ጥረት የአሁኑ አየር ኃይል አባላት ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ተናግረዋል፡፡ በሸራተን አዲስ በሚካሄድ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በሚገኘው ገቢ መጽሐፉን ለማሳተም እቅድ መያዛቸውን የገለፁት አመራሮቹ፤ መጽሐፉ ገበያ ላይ ውሎ የሚገኘውን ገቢ ለአየር ኃይል ቬንተራንስ አሶሴየሽን ማቋቋሚያና ማደራጃ ለማዋል ማሰባቸውንም ተናግረዋል። ከገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም 20 ሚሊዮን ብር እንደሚጠብቁም አመራሮቹ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።

Published in ዜና

የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ በከባድ ሙስና ወንጀል ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠውን የቀድሞው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሠ መስተዳደር አቶ ያረጋል አይሸሹምን ጨምሮ በሁሉም ተከሣሾች ላይ የሚወሠነው ቅጣት እንዲከብድ ጠየቀ፡፡ አቃቢ ህግ ጉዳዩን ሲከታተል ለቆየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛው ወንጀል ችሎት በፅሁፍ ባቀረበው የቅጣት አስተያየት፤ በአንድ ክስ ጥፋተኛ የተባሉት አቶ ያረጋል እና በሶስት ክሶች ጥፋተኛ የተባሉትን የቀድሞው የክልሉ ም/ቤት አፈ ጉባኤ እና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃብታሙ ሂካ እንዲሁም በመጀመሪያው ክስ 3ኛ እና 4ኛ ተከሣሽ ሆነው ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠው፡፡ አቶ ጌድዮን ደመቀ እና አቶ አሠፋ ገበየሁ ላይ ቅጣቱ ይክበድልኝ ሲል አመልክቷል፡፡ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶቹም 1ኛ እና 2ኛ ተከሣሽ ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው በመሆኑ፣ 3ኛ እና 4ኛ ስልጣን ባይኖራቸውም በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆናቸውና የቅጣት እርከኑም ከፍተኛ ስልጣን ባላቸው ስር የሚታይ በመሆኑ እንዲሁም ሁሉም ተከሣሾች በመንግስት ላይ ከባድ አላማ በመያዝ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ያደረሡ በመሆናቸው የሚሉት ናቸው፡፡ በተመሣሣይ አቃቤ ህግ ከ2ኛ እስከ 3ኛ ባሉት ክሶች ጥፋተኛ የተባሉት ሁሉም ተከሣሾች በከፍተኛ ስልጣን፣ በጣም ከፍተኛ ጉዳት እና ከባድ አላማ በሚሉ የወንጀል ደረጃ መግለጫዎች እንዲያዝለት በቅጣት አስተያየቱ አመልክቷል፡፡ ቅጣቱ በሁሉም ተከሣሾች ላይ እንዲከብድለት የጠየቀው አቃቤ ህግ አቶ ሃብታሙ ሂካ፣ አቶ ጌዲዮን ደመቀ፣ አቶ አሠፋ ገበየሁ በ3 ግዙፍ ክሶች ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠ በመሆኑ የእያንዳንዱ ክስ የቅጣት ውሣኔ ከተላለፈ በኋላ የእስራትና የገንዘብ መቀጮው ተደምሮ እንዲወሠን አመልክቷል፡፡ በአንድ ክስ ብቻ ጥፋተኛ የተባሉት አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ የጋድ ኮንስትራክሽን ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ አድገህ፣ የየኮለን ኮንስትራክሽን ስራ አስኪያጅ አቶ መክብብ ሞገስ ላይም ቅጣቱ ከብዶ እንዲወሠን አቃቤ ህግ ጠይቋል፡፡ ፍ/ቤቱም የተከሣሾችን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ለመቀበል መዝገቡን ለታህሣስ 15 ቀጥሯል፡፡

Published in ዜና

ከአንድ ወር በፊት በሀዋሳ ከተማ የመኪና አደጋ ደርሶበት በኮሪያ ሆስፒታል እየታከመ ላለው ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ፣ የገንዘብ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራም እንደሚዘጋጅ የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጋዜጠኛ አያሌው አስረስ ገለፁ፡፡ የእራት ምሽቱ የሚዘጋጀው አትላስ ሆቴል አካባቢ በሚገኘው “ኦካናዳ” ባርና ሬስቶራንት ውስጥ ሲሆን፤ የሃሳቡ አመንጪዎች የሬስቶራንቱ ባለቤቶች እንደሆኑም ሰብሳቢው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ታህሳስ 7 እና 8 ከ11 ሰዓት ጀምሮ የሚካሄደው የራት ምሽት መግቢያው 500 ብር ሲሆን የፋሽን ትርኢትና በዲጄ ሳሚ የሚዘጋጅ የሙዚቃ ግብዣንም ያካትታል ተብሏል፡፡

“ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነን ከጉዳቱ ለመታደግ ፈቃደኛ ግለሰቦች ድጋፍ ቢያደርጉም ወጭውና የሚሰበሰበው ገንዘብ ሊመጣጠን አልቻለም” ያሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ፤ በዚህ ምክንያት ተጨማሪ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ገልፀዋል፡፡ በእራት ምሽቱ ከ250 በላይ ሰዎች እንደሚጠበቁና ከ80ሺህ ብር በላይ ለመሰብሰብ እንደታቀደ ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡ የ“ኦ ካናዳ” ባርና ሬስቶራንት ባለቤት ወ/ሮ ሊሊ ካሳሁን በበኩላቸው፤ ከእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴው ጋር በመተባበር ልዩ የእራት ምሽቱን እያዘጋጁ እንደሆነ ገልፀው፤ ህብረተሰቡ የመጀመሪያዎቹን ትኬቶች በመግዛት ለጋዜጠኛው ወገንተኛነታቸውን እንዲገልፁ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አያሌው አስረስ በበኩላቸው ሃሳቡን በማፍለቅና ተነሳሽነት በማሳየት የእራት ምሽቱን ለማዘጋጀት የፈቀዱትን የ“ኦ ካናዳ” ባርና ሬስቶራንት ባለቤቶችን አድንቀው፣ የራት ምሽቱን ትኬቶች በሬስቶራንቱና ሌሎች ቦታዎች በመግዛት ህብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ካስተላለፉ በኋላ ኮሚቴው ሌሎች የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡” ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ “የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት አባል በሙስና እጅ ከፍንጅ ተያዘ” በሚል ርዕስ በኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ላይ ባወጣው ዘገባ የተነሳ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጣውና በአዘጋጆቹ ላይ ክስ መመስረቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ጋዜጠኛው ፍ/ቤቱ ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ወደ ሀዋሳ በተጓዘበት ወቅት በደረሰበት የመኪና አደጋ በአከርካሪውና በሳንባው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት በኮሪያ ሆስፒታል እየታከመ ይገኛል፡፡

Published in ዜና

ከቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አስተዳደር ልዩ ቦታው ስፖርት ኮሚሽን እየተባለ በሚጠራ አካባቢ የሚኖሩ 534 አባወራዎች ሥፍራው የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ የሚካሄድበት በመሆኑ ቤታቸውን በሰባት ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ የተሰጠውን ውሣኔ በመቃወም አቤቱታቸውን ለከንቲባው ፅ/ቤት ማቅረባቸውን ገለፁ፡፡ የክፍለ ከተማው አስተዳደር የወረዳ 3 ፅ/ቤት ለእነዚሁ ነዋሪዎች የሰጠው ደብዳቤ፤ ሥፍራው ለብሔራዊ ስቴዲየም ግንባታ የተመረጠ እንደሆነና ነዋሪዎቹ ሥፍራውን ያለ አግባብ ወሮ በመያዝ የልማት ሥራው እንዲዘገይ ማድረጋቸውን ጠቅሶ፤ በሰባት ቀናት ውስጥ ንብረታቸውን በማንሣት የልማቱ ተባባሪ እንዲሆኑ ይጠይቃል፡፡ የአስተዳደር ፅ/ቤቱ ስለ ጉዳዩ ከ6 ወራት ጀምሮ ለነዋሪዎቹ ማሳወቁንም በደብዳቤው ላይ ጠቁሟል፡፡ 534 አባወራ ነዋሪዎቹ ለከንቲባው ፅ/ቤት ባቀረቡት የቅሬታ አቤቱታ ላይ እንደገለፁት፤ ቀደም ሲል የክፍለ ከተማው ምክትል ሥራ አስፈፃሚና የመሬት ልማት ባንክ ፅ/ቤት ኃላፊ፣ የአካባቢውን ህዝብ ሰብስበው እስከ አዲሱ ሊዝ ስሪት አዋጅ ድረስ የተያዙ ይዞታዎች በሙሉ በሰነድ አልባ ፕሮግራም በየደረጃ የሚስተናገዱ መሆኑን እንደነገሯቸው ጠቅሰው፤ አሁን በድንገት በሰባት ቀናት ውስጥ ቤታቸውን እንዲለቁ መጠየቁ አግባብነት የለውም ብለዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በአብዛኛው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ የገለፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ለአመታት የኖርንበትን ቤት በሰባት ቀናት ውስጥ ለቀን ህፃናት ልጆቻችን ይዘን የምንሄድበት አቅም የለንም ብለዋል፡፡ የአገሪቱን የልማት እንቅስቃሴዎች እንደግፋለን የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ ሆኖም እኛም ዜጐች እንደመሆናችን መጠን መንግስት ለልማት ተነሺዎች በሚያመቻቸው ዕድል ተጠቃሚዎች ልንሆን ይገባል ብለዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ለከንቲባው ፅ/ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ምላሽ ከማግኘቱ በፊት ከቤታቸው እንዳይፈናቀሉም ተማፅነዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደር ለልማት ተነሺ የሆኑ ዜጐችን ባላቸው መረጃ መሰረት እያስተናገደ እንደሚገኝና እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ያሉ ይዞታዎች ህጋዊ ሠነድ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ተተኪ ቦታና ካሳ እየከፈለ ሲሆን የ2003 ካርታ በመመሪያው እንዳልተካተተና እነዚህ ዜጐችም መመሪያው የማይደግፋቸው ከሆነ ለማስተናገድ እንደማይቻል የመሬት አስተዳደር ቢሮው አመልክቷል፡፡ ከንቲባው ለአቤቱታቸው የሚሰጡትን ውሣኔ እየተጠባበቁ እንደሆነም ነዋሪዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።

Published in ዜና
Page 15 of 16