• በአገሪቱ ጉብኝት ያደርጋሉ

ባን ኪ.ሙንን ጨምሮ መቀመጫቸውን ሮም ያደረጉ ሶስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ሰኞ አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ በተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ ባን ኪ ሙን የሚመራው የልዑካን ቡድን ከሰኞ እስከ ረቡዕ በሚያደርጉት ጉብኝት ሀዋሳ ላይ በተባበሩት መንግስታት በገንዘብ የሚደገፉ ፕሮጀክቶችን ሁኔታ ይገመግማሉ የተባለ ሲሆን በተለይም በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል ያሉ ህዝቦች በድርጅቶቹ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው በምግብ ዋስትናና በድህነት ቅነሳ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ማጠናከር ላይ ይመክራሉም ተብሏል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ በታንዛኒያ ጉብኝቱን እንደሚያደርግ የተገለፀ ሲሆን ለጉብኝቱ ኢትዮጵያና ታንዛኒያ የተመረጡበት ምክንያት የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP)፣ የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) እና መሰል የመንግስታቱ ድርጅቶች በድህነት ቅነሳና በምግብ ዋስትና ላይ በገንዘብ የሚደገፉ ፕሮጀክቶች ስላሏቸው እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ ከዲሴምበር ዘጠኝ እስከ ዲሴምበር 11 ቀን 2013 በአዲስ አበባና በሀዋሳ ቆይታ የሚያደርጉት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ ባን ኪ ሙን እና አጋሮቻቸው ማክሰኞ ምሽት በሸራተን አዲስ ሆቴል በ11 ሰዓት ለጋዜጠኞች ስለ ጉብኝቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ረቡዕ ወደ ታንዛኒያ እንደሚያቀኑ አዲስ አበባ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

Published in ዜና

ዱባይ ውስጥ በቤት ሰራተኝነት የተቀጠረች ኢትዮጵያዊት፣ የ12 አመት እድሜ ካለው የአሰሪዎቿ ልጅ ጋር በመፈፀመችው ወሲብ አርግዛለች በሚል የተከሰሰች ሲሆን፣ ሁለቱም የ6 ወር እስር እንደተፈረደባቸው አጅማን የተሰኘ የዜና ተቋም ዘገበ፡፡ ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈፀም በተባበሩት የአረብ ኢሜሬቶች ህግ ያስጠይቃል በሚል የተከሰሰችው ኢትዮጵያዊት፣ የተፈረደባትን የእስር ቅጣት ስትጨርስ ወደ አገሯ ትባረር እንደሆነ የተዘገበ ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያዊቷ እርግዝና ሊታወቅ የቻለው በአጋጣሚ መሆኑን ዘገባው ገልፆ፣ ልጃቸውንና የቤት ሰራተኛቸውን ቤት ውስጥ ትተው የወጡ ወላጆች ድንገት ሲመለሱ ጉድ እንደጠበቃቸው ያወሳል፡፡ የ12 አመቱ ልጃቸው፣ መኝታ ክፍሉ ውስጥ ከ28 አመቷ ኢትዮጵያዊት ጋር ወሲብ እየፈፀመ ደርሰው የተመለከቱ ወላጆች ዝም አላሉም፡፡ ድርጊቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈፀመ ጉዳይ እንዳልሆነ ያረጋገጡት ግን፣ ኢትዮጵያዊቷ በሆስፒታል ምርመራ እርጉዝ መሆኗ ከታወቀ በኋላ ነው ብሏል ዘገባው፡፡ ፖሊስ በታዳጊውና በቤት ሰራተኛዋ ላይ ክስ ካቀረበ በኋላ፣ ፍ/ቤት በሁለቱም ተከሳሾች ላይ የስድስት ወራት እስር ፈርዶባቸዋል፡፡ የታዳጊው ጠበቃ፣ ደንበኛዬ ከ18 አመት በታች ስለሆነ ክሱ ተሻሽሎ ቅጣቱ ሊቃለልለት ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሰራተኛ ከቤተሰቡ አባላት ጋር ፀብ ስለነበራት ተንኮል ሰርታለች በማለት መከራከሪያ ያቀረበው ይሄው ጠበቃ፤ ያረገዘችው ከሌላ ሰው ስለሆነ ወደ አገሯ እንዳትባረር ሰግታ ነው በታዳጊው ላይ ሸር የሰራችው በማለት ለማሳመን ሞክሯል፡፡ ጠበቃው በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ባይቀናውም በይግባኝ ልጁን ነፃ እንዳስለቀቀ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

Published in ዜና

ሁሉም እርግዝና የተፈለገ መሆን አለበት፡፡
ሁሉም እርጉዞች በሰለጠነ የሰው ኃይል ሊወልዱ ይገባል፡፡
ሁሉም ጨቅላ ሕጻናት በህክምና ባለሙያ ሊወለዱ ይገባል፡፡
ሁሉም ሴቶች በራሳቸውም ይሁን በልጆቻቸው ጤና ላይ ..በእርግዝና ፣መውለድ እና ከወሊድ በሁዋላ.. ችግር

ሲገጥማቸው በስራ ላይ ያለ እና የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ የህክምና ተቋም በቅርባቸው እና በቀላሉ ሊያገኙ

የሚችሉበት መንገድ መመቻቸት አለበት፡፡
ጥንቃቄ የተደረገለት እርግዝና፣ ልጅ መውለድ እና እናትነት መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ነው፡፡
ከላይ ያነበባችሁት የዘንድሮውን የአለም የኤችአይቪ ኤይድስ ቀን ምክንያት በማድረግ የአለም የጤና ድርጅት ድህረገጽ

ለንባብ ያበቃው ነው፡፡ የአለም ኤችአይቪ ቀን ህዳር 22/ 2006 ዓ/ም ተከብሮ የዋለ ሲሆን የዚህ ቀን በየአመቱ መከበር

አላማም ሀገራት እንዲሁም ህዝቦች በየጊዜው የበሽታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ የአሰራር ስልቶቻቸውን እያሻሻሉ

ስለእውነታው በግልጽ እየተወያዩ ህዝብን ከበሽታው ስርጭት ማዳንና ለወደፊቱ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ትውልድን

ለማፍራት ነው፡፡
የአለም ኤችአይቪ ኤይድስ ቀን የዘንድሮው መሪ ቃል “Shared responsibility: Strengthen Results for an AIDS

– Free Generation.”  የሚል ነው፡፡ ሀላፊነትን መጋራት እና ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ትውልድን ማፍራት የአለም ሀገራት

ሊያተኩሩበት የሚገባ ትልቅ የስራ ድርሻ መሆኑን እ.ኤ.አ የ2013/ የኤድስ ቀን መሪ ቃል ያሳስባል፡፡
የአለም ኤድስ ቀን መከበር የጀመረው እ.ኤ.አ ከ1988 /ማለትም ከዛሬ 25/ አመት ጀምሮ ሲሆን ሀሳቡን ያፈለቁትም

እ.ኤ.አ በ1987/ James W.Bunn & Thomas Netter የተባሉ በጊዜው በአለም የጤና ድርጅት ውስጥ በጄኔቭ

ኤይድስን በሚመለከት መረጃን ለህዝብ ያደርሱ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ሰዎች ሀሳባቸውን ዛሬ UNAIDS

በሚባለው መስሪያ ቤት በዚያን ጊዜ የአለም አቀፉን ፕሮግራም ለሚመሩት Dr. Jonatahan Mann  ዲሴምበር 1

/የአለም አቀፍ የኤይድስ ቀን ተብሎ ሊታሰብ ይገባል ባሉት መሰረት ሀሳባቸው ተቀባይነትን አግኝቶ እነሆ በመከበር ላይ

ይገኛል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት  ድህረ ገጽ እንደሚገልጸው እ.ኤ.አ በ2009 ወደ 400.000 የሚሆኑ ህጻናት አዲስ በቫይረሱ

መያዛቸውን እና ከዚህም ወደ 90 ኀ ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ከእናት ወደ ልጅ በመተላለፍ ነው፡፡ ኤችአይቪ ቫይረስ

ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ አስፈላገው ስራ ካልተሰራ ከ20 -45% የሚሆኑት የሚወለዱ ልጆች በቫይረሱ ሊያዙ

የሚችሉ ሲሆን ከነዚህም አብዛኞቹ የሁለተኛውን አመት የልደት በአላቸውን ሳያከብሩ ህይወታቸው ያልፋል፡፡ ከዚህም

በላይ በቫይረሱ ከተያዙት እርጉዝ ሴቶች 42ቴ000-60ቴ000 የሚሆኑት ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡ ይህ መረጃ

የሚያመለክተው ባላደጉት ሀገራት በተለይም ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ያለውን እውነታ ሲሆን የበለጸጉት

ሀገራት እውነታ ግን በፍጹም ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ባደጉት አገራት አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ህጸናት እና በቫይረሱ

ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ቁጥር ወደ ዜሮኀ  ወርዶአል፡፡ ስለዚህም ህጻናቱ በቫይረሱ እንዳይያዙ እና እናቶችም

በቫይረሱ እንዳይጎዱ ማድረግ ይቻላል ይላል የአለም የጤና ድርጅት መረጃ፡፡ በ2015 / በአፍሪካ ከሚጠበቁት የልማት

ግቦች መካከል የእናቶችና የህጻናት ጤንነት መሻሻል የሚገኝበት ሲሆን በተለይም ከኤችኤይቪ ጋር በተያያዘ ሁለት

መሰረታዊ ነጥቦችን ያካተተ ነው፡፡
አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ህጻናትን ቁጥር በ2009 /ከተመዘገበው በ90 ኀ ያህል መቀነስ
ከኤችአይቪ ኤድስ ጋር በተያያዝ የሚከሰቱ የእናቶችን ሞት በ50%  መቀነስ የሚሉ ናቸው፡፡
ከላይ የተገለጸው መረጃ አለም አቀፍ ገጽታ ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ ከኤችአይቪ ኤይድስ ጋር በተዛመደ ሜይ 30/2013

የወጣ መረጃ የሚከተሉትን  እውነታዎችን ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ወደ 86/ ሚሊዮን የሚጠጋ ሲሆን በየአመቱ እንደሚገመተው ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ወደ

759ቴ268 ይጠጋል፡፡ ከዚህም ውስጥ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ እርጉዝ ሴቶች ቁጥር ወደ 34ቴ524 ይደርሳል፡፡
የኤችአይቪ ስርጭትን በሚመለከት መረጃው እንደሚጠቁመው ባብዛኛው በእድሜያቸው ከ15-24 የሚደርሱ ወጣቶች

በቫይረሱ እንደሚያዙ ነው፡፡ትልልቅ ሰዎችን በሚመለከት 1.5% ያህል በቫይረሱ የሚያዙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ወንዶች

1% ሴቶች ደግሞ 1.9 % ይሆናሉ፡፡ የኤችኤቪ ቫይረስ ስርጭት 2.4 % ያህሉ እርጉዝ ሴቶችን የሚመለከት ነው፡፡
ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ በኢትዮጵያ በመሰራት ላይ ያለውን ተግባር የሚመለከተው

ይህ የመረጃ ገጽ እንደሚጠቁመው ወደ 33.4% የሚሆኑ እርጉዝ ሴቶች የኤችአይቪ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን ጸረ

ኤችአይቪ መድሀኒትን በመጠቀም ረገድ በ2012/ ወደ 41% ያህል እንደሚደርሱ ተጠቁሞአል፡፡ በኢትዮጵያ ከቫይረሱ ጋር

ለሚኖሩ እርጉዝ እናቶች የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት ሽፋን እስከ 45% የሚደርስ መሆኑም ተገልጾአል፡፡ ከእናት ወደልጅ

ቫይረሱ የመተላለፉ ሁኔታን መረጃው እንደሚጠቁመው በ2011/ ወደ 30% ያህል ሲሆን በ2012 ደግሞ ወደ 20% ዝቅ

ብሎአል፡፡ ስለዚህም የህክምናው ክትትልና የህብረ ተሰቡ ንቃተ ህሊና ባደገ እና በጨመረ ቁጥር ከቫይረሱ ነጻ የሆነ

ትውልድን የማፍራት ሂደቱ በተወሰነለት የጊዜ ገደብ ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
እ.እ.አ 2013/ ዲሴምበር 1/ የተከበረውን ኤችአይቪ ኤይድስ ቀን ምክንያት በማድረግ የወጡ የተለያዩ መረጃዎች

እንደሚጠቁሙት...
በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ኢትዮያን ጨምሮ ወደ 9.7 ሚሊዮን ሰዎች ፀረኤችአይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1981 እና 2007/መካከል ኤይድስ 25 ሚሊዮን ሰዎችን ለህልፈት ዳርጎአል፡፡
በ2012/በአለም ወደ 35.3 ሚሊዮን ሰዎች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ይገመታል
ከሰሀራ በታች ያሉ ሐገራት ሕዝቦች ይበልጡን በቫይረሱ እንደሚጎዱ የታወቀ ሲሆን ከ20 ሰዎች መካከል አንዱ

በቫይረሱ እንደሚያዝ ይገመታል፡፡
በአለማችን ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ ሰዎች  ወደ 69% የሚሆኑት ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት የሚገኙ ናቸው፡፡
ኤችአይቪ ለጊዜው ጭርሱንም ባይድንም ነገር ግን በህክምና እና በአኑዋኑዋር ዘዴ ሊረዳ የሚችል ነው፡፡
የተለያዩ መረጃዎች ለንባብ ካበቁዋቸው እውነታዎች የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
እ.ኤ.አ በ2012 ዓ/ም 35.5/ ሚሊዮን ሰዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ታውቆአል፡፡ የቫይረሱ

ስርጭት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ 75/ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
አዲስ በኤችአይቪ ቫይረስ የሚያዙትን በሚመለከት መረጃው እንደሚጠቁመው
እ.ኤ.አ ከ2001 ወዲህ በ33% ቀንሶአል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ 2.3 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ አዲስ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ይህም ቀደም ሲል ከነበረው

ዝቅ ብሎ የሚገኝ ነው፡፡
በአደጉ እና በታዳጊ ሰዎች ላይ የቫይረሱ መከሰትን በሚመለከት ከ26/ በሚበልጡ ሀገራት እንደታየው በ2001 እና 2012

መካከል በ50% መቀነሱ ተመዝግቦአል፡፡
ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሞትን በሚመለከት
እ.ኤ.አ በ2005 ከተመዘገበው 30% ያህል ቀንሶ ይገኛል፡፡
በ2012/ ወደ 9.7 ሚሊዮን ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን ይህም በማደግ

ላይ ባሉ ሀገራትና በመካከለኛ ደረጃ ባሉ ሀገራት ነው፡፡ ከነዚህ 61 ኀ የሚሆኑት ተጠቃሚ የሆኑት በ2010 /የአለም

የጤና ድርጅት ባወ ጣው መመሪያ መሰረት ሲሆን 34% የሚሆኑት ሰዎች ደግሞ ተጠቃሚ የሆኑት አሁ ንም የአለም

የጤና ድርጅት በ2013/ባወጣው መመሪያ መሰረት ነው፡፡
ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ከቲቢ በሽታ ጋር በተያያዘ የሚኖረው ሞት ከ2004/ጀምሮ ወደ 36% ቀንሶ

ተመዝግቦአል፡፡  ቲቢ አሁንም በኤይድስ ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ለሞት በማብቃት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡
 አለም አቀፉ መድረክ እንደተስማማበት እ.ኤአ እስከ 2015 ድረስ ከእናት ወደልጅ የሚተላለፈው ኤችአይቪ ቫይረስ እና

እናቶች በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸው እንዲቀንስ ማስቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ ስምምነት መሰረት ፕሮግራሙን

ተቀብላ ህዝቦችዋን ለማዳን ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑዋ እሙን ነው፡፡ የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች

ማህበር በበኩሉ በተለያዩ መስተዳድሮች አዲስ አበባን ጨምሮ ከግል የህክምና ተቋማት ጋር በመሆን ኤችአይቪ ከእናት

ወደልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን ፕሮጀክት ካለፉት አራት አመታት ወዲህ በማስፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ ከቫረሱ ነጻ

የሆነ ትውልድን ለማፍራት አጋር ድርጅቶችም የበኩላቸውን እገዛ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ 

Published in ላንተና ላንቺ

“የተመረጠው ቦታ ለፀጥታ ጥበቃ አመቺ ባለመሆኑ እውቅና ለመስጠት እንቸገራለን”
አዲስ አበባ መስተዳድር
-    ኢ/ር ይልቃል በጄኔቭ ከአይኦኤም፤ ከአይኤልኦ እና ከሂውማን ራይትስ ዎች ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ

ሰማያዊ ፓርቲ አፄ ምኒልክ ያረፉበትን መቶኛ አመት ለማክበር ካዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ውስጥ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽንና

የፓናል ውይይቱን ታህሳስ ስድስት ቀን በጃንሜዳ ለማድረግ ቢያቅድም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላማዊ ሰልፍና

ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል እውቅና እንደከለከለው ፓርቲው አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል በበኩሉ፤ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽንና የፓናል

ውይይት ለማካሄድ የተመረጠው ቦታ ለፀጥታ ጥበቃ አመቺ ባለመሆኑ በፓርቲው የተጠየቀውን እውቅና ለመስጠት

እንደሚቸገር በፃፈው ደብዳቤ ለፓርቲው አሳውቋል፡፡
ፓርቲው በበኩሉ፤ በጃንሜዳ የምናካሂደው የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽንና የፓናል ውይይት በመሆኑ ብዙ እንቅስቃሴ

የለውም፣ ጃንሜዳም ቢሆን ለፀጥታ አስጊ ቦታ አይደለም፤ ስለዚህ መስተዳድሩ እውቅና ላለመስጠት ያቀረበው ምክንያት

የህግ ድጋፍ የለውም በመሆኑም፤ ፕሮግራሙን በጃንሜዳ አካሂዳለሁ ሲል ለመስተዳድሩ ደብዳቤ ፅፏል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አቶ ብርሀኑ ተክለ ያሬድ፣ መስተዳድሩ እውቀና የከለከለበትን ምክንያት ለምን ፓርቲያቸው

እንዳልተቀበለው ሲያስረዱ፣ ከዚህ በፊት መስተዳድሩ ቦታውን ለሰላማዊ ሰልፍ መፍቀዱን አስታውሰው፣ አሁን ለፓናል

ውይይት እውቅና መከልከሉ ጽ/ቤቱ በህግ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ የዜጐችን የመሰብሰብ መብት የሚገድብ በመሆኑ

ፓርቲያቸው እንደማይቀበለውና ፕሮግራሙን በዕለቱ በቦታው እንደሚያካሂድ፤ ይህንንም ለመስተዳድሩ በደብዳቤ

ማሳወቁን አቶ ብርሀኑ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ባለፈው አርብ ወደ ጀርመን አቅንተው የነበሩት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤

ከትላንት በስቲያ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የተገኙ ሲሆን ከአለም የስደተኞች ድርጅት (IOM)፣ ከአለም የስራ ድርጅት (ILO)

እና ከሂውማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል፤ በጄኔቫ የሚገኙ የፓርቲው

ደጋፊዎች ከትላንት በስቲያ ከሶስቱ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በተለይም በወቅቱ የኢትዮጵያውያን ስደተኞችና የሳኡዲ

መንግስት ድርጊት ላይ በሰፊው እንደተወያዩ የፓርቲው አመራሮች ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አይኦኤም ወደ ኢትዮጵያ ለተመለሱ ኢትዮጵያውያን የመጠለያ፣ የልብስና ወደ ቤተሰቦቻቸው መጓጓዣ

ጭምር ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑ፣ ከአይኦኤም ጋር ቀይ መስቀልና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች እየተባበሩ እንደሆነ

ለስደተኞቹ ማጓጓዣ የሳኡዲ መንግስት አውሮፕላኖችን ስለመመደቡና እስካሁንም አይኦኤም አምስት ሚሊዮን ዶላር

ስለማውጣቱ፣ የድርጅቶቹ ከፍተኛ አመራሮች ለኢ/ር ይልቃል ነግረዋቸዋል ተብሏል፡፡ አይኦኤም በቀጣይ 13 ሚሊዮን

ዶላር ለኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መመደቡን ለሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የገለፁላቸው ሲሆን ከዚህ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ

ስለሚመለሱትና እስካሁን ስለተመለሱት ስደተኞች አይኦኤም፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የሳኡዲ መንግስት ትክክለኛው

መረጃ እንደሌላቸው ሶስቱ አለም አቀፍ ድርጅቶች ለኢ/ሩ መግለፃቸው ተጠቁሟል፡፡  

Published in ዜና
Page 16 of 16