መንግሥት የደረሰው ጉዳት እየተጣራ መሆኑን አስታውቋል

    በባህርዳር የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መንግስት ካሳ እንዲከፍልና ጥቃቱን የፈፀመውን አካል ለፍርድ እንዲያቀርብ መድረክ የጠየቀ ሲሆን መንግሥት በበኩሉ ጉዳቱ እየተጣራ ነው ብሏል፡፡ “በባህርዳር ከተማ በሰላማዊ አግባብ ተቃውሞ ባሰሙ ዜጎች ላይ የተፈፀመው ጥቃት የአምባገነናዊ አገዛዝ ባህሪ ነፀብራቅ ነው” ያለው ፓርቲው፤ ማንኛውንም የኃይል እርምጃ በጥብቅ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪ በሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ላይ የተወሰደው የኃይል እርምጃ በህገ መንግስታዊ የመቃወም መብት ላይ የተፈፀመ ጥሰት ነው ያለው መድረክ፤ ከዚህ ቀደምም የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታይ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ መሰል ተግባር ሲፈፀም መቆየቱን ጠቅሶ፤ “ጥቃቱ ኃላፊነት የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲል አውግዟል፡፡ በሌላ በኩል በደቡብ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የመድረኩ አባላት በማዳበሪያ እዳ ሰበብ እየታሰሩ እንደሆነ የጠቆመው ፓርቲው፤ ድርጊቱ የሚፈጸመው አባላቱን ከግንቦቱ የምርጫ እንቅስቃሴ ለማራቅ በማሰብ ነው ብሏል፡፡ በባህርዳር ከእምነት ቦታ ጥያቄ ጋር በተገናኘ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ጉዳት ስለ መድረሱና ስለ እርምጃው ተገቢነት ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ጉዳት ስለመድረሱ መረጃው እንዳላቸው ጠቁመው የጉዳቱ ምክንያት ምንድን ነው የሚለው ተጣርቶ እንደሚታወቅ ተናግረዋል፡፡ “በፀጥታ ኃይሎች ነው የተከናወነው ወይስ የተለያየ የራሱ መንገድ አለው የሚለው ተጣርቶ የሚታወቅ ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ጉዳዩ ተጣርቶ ውጤቱ በሚታወቅ ጊዜ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል፡፡


Published in ዜና

ትብብሩ ለሁለት ወሩ እንቅስቃሴ የ1.2 ሚ. ብር በጀት አፅድቋል
-    የሰማያዊ ፓርቲ የክልል አመራሮች የአመራር ክህሎት ስልጠና እየወሰዱ ነው
  የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር የ“ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” ሁለተኛ ዙር የተግባር እንቅስቃሴ ፕሮግራሙን በትላንትናው እለት ይፋ ያደረገ ሲሆን ለሁለት ወር እንቅስቃሴው ማስፈፀሚያ የ1.2 ሚሊዮን ብር በጀት አፅድቋል፡፡ በሌላ በኩል የሰማያዊ ፓርቲ የክልል አመራሮች ካለፈው እሁድ ጀምሮ ጠቅላላ የአመራር ክህሎት ሥልጠና በፓርቲው ጽ/ቤት እየወሰዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ትናንትና በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ሁለተኛ ዙር ፕሮግራሙን ይፋ ባደረገበት ወቅት፤ በመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴ ከጎኑ በመቆም አላማውን ለደገፉ በአገር ቤትና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን “ትግሉን ለማደናቀፍና ትግላችንን ለመግታት ለሰላማዊ ዜጋ ቀርቶ ለጠላት የማይገባ ኢ-ህገ-መንግስታዊ ተግባር ለፈፀማችሁ የመንግስት አካላት ወደ ህሊናችሁ እንድትመለሱ ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል፡፡
የትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ በእለቱ በሰጠው መግለጫ፤ በቀጣዩ ሁለት ወራት አዲስ አበባን ጨምሮ በ15 ተመረጡ ከተሞች ላይ የተለያዩ የአዳራሽና የአደባባይ ህዝባዊ ውይይቶች፣ ሰላማዊ ሰልፎችን እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡ የእንቅስቃሴዎቹ አላማ ቀጣዩን ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓዕማኒና አሳታፊ እንዲሆን መንግስት የጠየቅናቸውን ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶ እንዲመልስ የሚያሳስብ ነው ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ፤ በተለይም የካቲት 15 በተመሳሳይ ሰዓት በ15ቱም ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚደረጉ ጠቁመዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴ የልማት ስራ በሚከናወንባቸው ቦታዎች ሰልፍ እየወጡ መንግስትን ይፈታተናሉ በሚል ከመንግስት ወቀሳ ቀርቦባችኋል በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ፤ “መንግስት ትግላችንን ለማወክና የህዝብ ድምፅ ለማፈን በርካታ እንቶ ፈንቶ ምክንያቶችን ሲደረድር ቆይቷል” ያሉት የትብብሩ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል፤ “ቀደም ሲል ቤልኤር ሜዳ  እና አበበ ቢቂላ ስታዲየም ህዝባዊ ውይይት ለማድረግ ጠይቀን ተከልክለናል፤  በኋላ እኛ ግን ተከለከልን ብለን ትግላችንን አናቆምም፤ አናፈገፍግምም” ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁከት ለማስነሳት ለሚጥሩ ፓርቲዎች ቀይና ቢጫ ካርድ ይሰጣቸዋል ማለታቸውን በተመለከተ አስተያየታቸውን ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ረጅም ታሪክና ባህል ላለው ህዝብ የሚመጥን አባባል አይደለም” በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን አባባል ያጣጣሉት ኢንጅነሩ፤ “እንደ አገርና እንደ ህዝብ የሚናገሩት ካለ እንጂ በአሁኑ ሰዓት ከእሳቸው ምክርም ትምህርትም የምንፈልግ አይደለንም፤ ቢጫና ቀይ ካርድ የሚለውም አነጋገር ለመረዳት ያስቸግረናል” ብለዋል፡፡
በቀጣዩ ምርጫ ትብብሩ ይሳተፍ እንደሆነ የተጠየቁት ኢ/ር ይልቃል፤ “በምርጫ ውስጥ ከሌለን እንዴት ምርጫው ፍትሃዊና ግልፅ ይሁን ብለን እንጨሃለን” ሲሉ በጥያቄ መልሰዋል፡፡ “የሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መሳሪያ ነው ብለን ስለምናምን በአግባቡ፣ ግልፅና ተአማኒነት በተሞላው መንገድ መከናወን አለበት፤ ያለበለዚያ ግን በምርጫው መሳተፍ ለህገ-ወጥነትና ለአገር ሀብት ብክነት መተባበር ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስትን መገዳደር አይችሉም” በሚል የሰነዘሩት ማስፈራሪያ አከል ንግግር ህዝብን ለማዳናገር የተፈጠረ ነው ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ፤ ከትግላቸው የሚያግዳቸው አንዳችም ነገር እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ባወጡት ባለ አራት ነጥብ መግለጫም የጉዳዩ ባለቤት ኢትዮጵያዊያን በሰላማዊ መንገድ ተፅአኖ በማሳረፍ መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ራሱን እንዲያዘጋጅ፣ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች የተጣለባቸውን አገራዊና ህዝባዊ ግዴታ ያለ አድልዎ በመወጣት ከታሪክ ተወቃሽነት እንዲድኑ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም የመግባቢያ ሰነዱ የጥናት ሪፖርት ላይ እስከመጨረሻው የነበሩ ከፓርቲ መሪዎች የግል ፍላጐትና ከፓርቲ ጥቅም የሚልቀውን የህዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት መጪው ምርጫ ፍትሃዊ ይሆን ዘንድ ከትብብሩ ጐን እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ50 በላይ የሚሆኑ የሰማያዊ ፓርቲ የአመራር አካላት ከባፈው እሁድ ጀምሮ በጠቅላላ የአመራር ክህሎት ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ስልጠናዎች እየወሰዱ ሲሆን ስልጠናው እስከመጪው እሁድ እንደሚቀጥል የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ የፓርቲው አመራሮቻች በክህሎት የዳበሩ፣ በእውቀት የበለፀጉና በቀጣዩ ሰላማዊ ትግል ህዝብን በማደራጀት፣ በማስተባበርና በማሳተፍ በኩል ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
 

Published in ዜና

አገሪቱ አምና ከጫት ኤክስፖርት ከ5 ቢ. ብር በላይ አግኝታለች
 
ጫት በዜጐች ላይ እያስከተለ ያለውን የጤና ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል የፖሊሲ አቅጣጫ ለመንደፍ ያለመ አገር አቀፍ የጫት ሲምፖዚየም በቅርቡ የሚካሄድ ሲሆን፣ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ታላላቅ የአገሪቱ ባለስልጣናት በሲምፖዚየሙ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
በአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና በትምህርት ቤቶች አካባቢ የጫት መሸጫና ማስቃሚያ ቤቶች በመበራከታቸው ምክንያት የመማር ማስተማሩን ሂደት በአግባቡ ለማከናወን አለመቻሉን የገለፁት የኢትዮጵ የምግብ የመድኀኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን አማካሪው አቶ መንግስተአብ ወልደአረጋይ፤ ሲምፖዚየሙ ጫት በዜጐች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት የሚያመላክቱ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡበትና ውይይት ተካሂዶ የፖሊሲ አቅጣጫ የሚነደፍበት ትልቅ ጉባዔ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡
ቀደም ሲል በህዝብ ተወካዮች አፈጉባዔ የሚመራና የክልል አፈጉባዔዎች የተሳተፉበት በአደገኛ መድሃኒቶችና ዕፆች ላይ ያተኮረ ሲምፖዚየም መካሄዱን ያስታወሱት አቶ መንግስተአብ፤ ጉባዔው በጫት ሳቢያ የሚደርሰውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ችግሮች ለመቅረፍና ዜጐችን ለመታደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ያደረገ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ጫት ወደ ውጪ አገር ተልከው የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ የአገሪቱ ምርቶች ተጠቃሽ መሆኑ አይካድም ያሉት አማካሪው፤ አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም በማሰብ ዜጐች ለከፋ ችግርና አደጋ ሲጋለጡ ዝም ብሎ ማየቱ ተገቢ ባለመሆኑ ሲሞፖዚየሙን ለማካሄድ እንደታቀደ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአውሮፓና አሜሪካ ያላት የጫት ሽያጭ በእጅጉ በመቀዛቀዙ ምርቶቿን በአብዛኛው የምትልከው ለየመን፣ ሶማሊያና አረብ አገራት ሲሆን ባለፈው ዓመት ጫት ከአገሪቱ የኤክስፖርት ምርቶች በአራተኛነት ደረጃ ላይ ሆኖ 270 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል፡፡

Published in ዜና

    ሲነበብ፥ እንደተገባደደም አእምሮ ዉስጥ የሚንገዋለል ልቦለድ ብርቅ ነዉ። በአንፃሩ ስሜት ለጥጦ ትረካዉ ሲደመደም የሚደበዝዝ የምንዘነጋዉ ያመዝናል። የአልበርት ካሙ “The Stranger” ወይም ሚፍታ ዘለቀ እንደተረጐመው፤ “ባይተዋሩ” ወደ ብዙ ቋንቋዎች የተመለሰና ከጥቂት የዓለም ምርጥ ልቦለዶች ጐራ የተመደበ ዘመናዊ ልጨኛ (classical) ነዉ። በመቶ ሃያ ሰባት ገፆች ተቀንብቦ 25 ብር የሚሸጠው ልቦለድ፤ አምና ታትሞ፣ ክብሩ መጻሕፍት መደብር አሁንም ያከፋፍለዋል። ዛሬ አንባቢ ተነፍጐ በ40 በመቶ ቅናሽ፣ ገዢ እያባበለ ለመፍዘዙ ምክንያቱ  ምን ይሆን? አንድም ተርጓሚው ስለ ካሙ ልቦለድ ጥልቀትና ኪነውበት እንደ መግቢያ ያተተው፥ ደራሲውንም ለማስተዋወቅ የፃፈው አለመኖሩ ነዉ፤ አንድም አከፋፋዩ  እስከ ዛሬ አያሌ ምሁራንን ያወያየና ያላተመ ልቦለድ መሆኑን ለማስተዋወቅ መትጋት እንዳለበት መዝንጋቱ ይሆናል። አልበርት ካሙ በሚመጥነው በጥሩ አማርኛ ለኛ አንባቢ ሲቀርብ፣ የፈረንሳይ ወይን ጠጅን የአበሻ አረቄ ስለተካው ተቆረፋፍዶ ተገለለ ብሎ ማፌዝ አይበጅም። በብዙ አልባሌ ትርጉም ስራዎች መጋረዱ ይቆጫል። ከዚህ በፊት መስፍን ዓለማየሁ የሄሚንግዌይን “ሽማግሌዉና ባህሩ”፣ ሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም የራልፍ ኤሊሰንን “የሀገር ልጅ”፣ ቴዎድሮስ አጥላዉ “አልኬሚስት” ... የመሳሰሉትን ድንቅ ልቦለዶች ቢተረጐሙም ትኩረት ሳይሰጣቸዉ፥ አንባቢ በጥሞና ሳይወያይባቸዉ ተጋርደዋል። ለመሆኑ Albert Camus ማን ነዉ?
ካሙ በሥነፅሁፍ የኖቤል ሽልማት የተበረከተለት ፈረንሳዊ ደራሲ ነዉ። እንደ የልቦለድ ደራሲ፥ ወግ ፀሐፊ፥ ጋዜጠኛና ፀሐፌ-ተዉኔት ስሙ የገነነ ነዉ። የብዕር ውጤቱ የህይወት ዘበትነት (the absurdity of life) የጠነነበት ቢሆንም ግለሰብ ለኑሮ ትርጉም ለመፍተል ሲጣጣርና ሲያቃስት ተተርኮበታል። ከሳርተር ጋር በህልውናነት ፍልስፍናና በማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም መጣጣምም መፋለስም ካሙ በአጭር እድሜው የኖረበት የተነፈሰበት ዐውድ ነዉ። ከሆነ ስፍራ በባቡር ለመሳፈር ሲጣደፍ ጓደኛዉ በሚኩና ካላደረስኩህ ብሎት እያሽከረከር ሲጓዝ በሌላ መኪና ይገጫሉ። ጓደኛዉ ሲተርፍ፥ ካሙ ግን በአደጋው ይሞታል። ልክ እንደ ፅሁፎቹ አሟሟቱም ፍልስፍናዉን -የሕይወት ዘበትነትን- አደመቀዉ። አያሌ ድንቅ ልቦለዶችና ተዉኔቶች ደርሷል። ከአንድ ሁለት ዐሰርት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር፣ጌታቸዉ ታረቀኝ፤ የካሙን እውቅ ተውኔት “Caligula” በውርስ ትርጉም ለመድረክ አብቅቶት ነበር፤ ዛሬ ሚፍታ ዘለቀ ከተረጐመው ልቦለድ “ባይተዋሩ” የተሻለ ተቀባይነት ነበረው። በተቀራራቢ ጊዜ ነበር ካሙ “ካሊጉላ” ተውኔት፣ “ባይተዋሩ” ልቦለድና እነዚህን ሁለቱን የፈጠራ ሥራዎቹን የደመቀበት ያጐላበት ዝነኛ ፍልስፍናዊ መጽሐፉን “የሲሲፈስ ሥነተረት” (The Myth of Sisyphus) ያሳተመው። በመጣጥፉ የኑሮን ዘበትነትና ሰው ለፖለቲካ፥ ለሃይማኖትና ለማህበራዊ እሴቶች ማጐብደድ ሣይሆን -nihilism- ግለሰባዊነትን መምረጡን ተንትኗል። ቀስ እያለ አልበርት ካሙ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ የትውልዱ አፈቀላጤ፥ የነገውን የፈረንሣይ፥ የአዉሮፓ ብሎም የዓለም አስተሳሰብና አዝማሚያ ጠቋሚ ሊሆን በቅቷል። ካሙ በስራዎቹ የክርስርትናና የማርክሲዝምን ቀኖናዊ አስተምህሮ እየተጋፈጠ፥ የዘመንተኞቹን በማህበራዊ እሴቶች የማመፅ -nihilism- አደጋ ቢያጣጥምም ለዕውነት፥ ለሀቅና ለሰከነ አቋም ከመሟገት አላፈገፈገም።
በግሪኮች ሥነተረት (ሚት) ሲሲፈስ ከሞተ በኋላ በሰማይ ቤት ሆኖ ምድር እጅጉን እየናፈቀው ለመንደሩ በቋጠረው ፍቅር ተንከራተተ፤ ልቡ ቃተተ። ለአንድ ቀን ብቻ አስፈቅዶ ከቀዬው ይመለሳል። ደስታ አብከነከነው፤ የኑሮ ጣዕሙ አልከስም አለ። የገባዉን ቃል አፍርሶ ከምድር ይቀራል። አማልክት በንዴት ይበግናሉ። እንደገና እስኪሞት ለአመታት ጠበቁት፤ ከመዳፋቸዉ ሲገባ እንዴት እንደሚቀጡት ካብሰለሰሉ በኋላ ይበየንበታል። አንድ ትልቅ አለት ከተራራ ሥር ሽቅብ እየገፋ ከተራራው ቋፍ እንዲያደርስ፥ ዝንተዓለም ይህን እንዲፈፅም ይፈረድበታል። ችግሩ አለቱን ገና ከተራራው ጫፍ እንዳዘለቀዉ ተንከባሎ ከነበረበት ሥፍራ ይመለሳል። ሲሲፈስ ረጅም መንገድ ተመልሶ እንደገና አለቱን መግፋት አለበት- ዝንተዓለም። Camus ሲሲፈስ ማለት የዘመናችን ሰው ነው፤ ዘመነኛ ሰው ዘወትር ይማስናል፥ ግን አያልፍለትም ባይ ነዉ። እንደ ሲሲፈስ ሽቅብ ሲባዝን፥ ቁልቁል ሲያዘቀዝቅ ይኖራል ከሚል ርዕዩት በመነሳት፣ ስለ ህይወት ዘበትነት -absurdity- በጥልቅ አውጠንጥኗል። ከሐያስያንና ምሁራን የሚበዙት፣ “ባይተዋሩ” ልቦለዱን የደረሰው ለሰው ህይወት ዘበትነት መግለጫ ነው ይላሉ። በእርግጥ ካሙ የግሪኩን የሲሲፈስን አፈ-ታሪክ፣ ግለሰብ የኑሮ ከንቱነቱ በእልህ ሲፋለም እንደ ተለዋጭ ዘይቤ -metaphor- ተጠቅሞበታል። እንደ ካሙ እምነት ከሆነ፣ የአንድ ግለሰብ የመጀመሪያ እርምጃ መሆን ያለበት የዚህን ዘበትነት እውነታ መቀበል ነው። ለሲሲፈስ -ለዘመነኛ ሰውም- የራስን ህይወት ማጥፋት መፍትሄ አይደለም፤ ብቸኛ ምርጫ ደስ እያለው አለቱን ሽቅብ በመግፋት ዘበትነት ላይ ማመፅ ነው ባይ ነው። የካሙ ተጨማሪ ክርክር ግለሰብ እየፈነደቀ ይህን የአለመሸነፍ ትግሉን እልሁን ሲወጣ እንደ ሰው ትርጉምና ማንነት ይጐናፀፋል። ሌሎች ደግሞ የሲሲፈስ -የዘመነኛ ሰው- ረብ ቢስ የሆነውን የአለት ሽቅብ መግፋት ከንቱ ድካም ሳይሆን የሚያሳስባቸዉ፥ አለቱ ተንከባሎ ረጅም ርቀት ከወረደ ባኋላ ዘመነኛ ሰው ቁልቁለቱን ሲወርድ ብቻውን ከራሱ ጋር በየዕለቱ የሚያውጠነጥነዉ ጉዳይ ነዉ፤ ምን እያብሰለሰለ ያዘግማል ? የመሰለ ጥያቄ እጅጉን አወያይቷል።
    “ባይተዋሩ” ልቦለድ በሁለት ክፍሎች ተዋቅሯል። ዋናው ገፀባህሪና ተራኪው መርሶ -meursault- በክፍል አንድ፣ ነፃ ሰው እያለ በሥራ ተጠምዶ በኋላም እናቱ ከአረጋውያን መጦሪያ ስለአረፉ ለቀብር ተጠርቶ፣ ተመልሶም ከውቧ ሴት ጓደኛው ሜሪ፣ ህይወትን ሲያጣጥም ባልጠበቀዉ ወቅትና ስፍራ ሳያስብበት አንድ አረብ ገድሎ ይያዛል። በዚህ ክፍል የጐረቤቶቹ ገመና፥ እና የእለት በእለት ህይወቱን አንዳንዴ እያውጠነጠነ፥ በሌላ ወቅት በዝምታ እንደ ገለልተኛ እያጤነ ያወጋል። በክፍል ሁለት መርሶ ሰው መግደሉን እንደ ቀላል ጉዳይ እየቆጠረ፣ ከወህኒ ቤት ለአስራ አንድ ወራት ያህል የፍርድ ቤት ውሳኔ እየጠበቀ ብቻውን ይታሰራል። የአደባባይ ኑሮ እየናፈቀው፥ ኢ-አማኝ በመሆኑም ምንም የመንፈስ የፈጣሪ እርዳታ ሳይለማመጥ ትናንቶቹን፥ ትዝታውን፥ የቤቱን ዕቃ ጭምር በእእምሮው እያመላለሰ የእስር ቤቱን የተንዛዛ ጊዜን ለመገድብ ይተጋል።“ቀጥሎ የተረዳሁት ነገር ቢኖር አንድ ቀን እንኳ በህይወት የኖረ ሰው እስር ቤት ቢገባ ከድብርት የሚያድኑት በቂ ትዝታዎች ስለሚኖሩት መቶ አመታትን በእስር መኖር እንደሚችል ነዉ” [ገፅ 81] ቀስ በቀስ የግሉን ውስጣዊ ህይወት ይበረብራል። በሁለቱም ክፍሎች በየገፁ የሚመስጡ ሁነቶች፥ እንግዳ ድርጊቶች፥ ከተቀበልነው አመለካከት ያፈነገጡ እሳቦቶች ይርመሰመሳሉ። ዝርዝር ሤራዉንና የሌሎች ገፀባህርያት ውጣውረዱን ለአንባቢ በማስተረፍ በደምሳሳው ስለ ባይተዋሩ ነጥቦች መቀስቀስ ይበቃል።
    ገና ከመነሻው መርሶ እውነትም ባይተዋር ይሆንብናል። እናቱን ለመቅበር ወደ አረጋውያን መጦሪያ ሲሄድ የሚያስተዛዝኑት እድሜዋን ቢጠይቁት አለማወቁን ይገልፃል፤ ማዘኑን አያሳውቅም። በማግስቱ ከሴት ጓደኛው ጋር አስቂኝ ፊልም አይቶ፥ ዋኝቶ ይዳራታል።
“ስንለባብስ ጥቁር ክራቫት መልበሴን በማየቷ የተገረመች መሰለችና ለቅሶ ሰንብቼ እንደሆን ጠየቀችኝ። እማዬ እንዳረፈች ነገርኳት። መች እንደሆነ ለማወቅ ፈለገች።
“ትላንት” አልኳት።
ትንሽ ደንገጥ ብትልም ምንም አልተናገረችም። የእኔ ጥፋት እንዳልሆነ ልነግራት ፈለግኩና ተውኩት። ... ባወራውም ምንም ትርጉም የለውም።” [ገፅ 21]
ማህበረሰቡ ከሱ የሚጠብቀውን ጉዳይ ለይሉኝታ እንኳን ማስመሰል አልፈቀደም። የተለያዩ ገፅታዎች በመለዋወጥ ታርቆ ማደር፣ ልክ አዳም ረታ በ “ይወስዳል መንገድ ...”  እንደቀረፃቸዉ ወይዘሮ አስካለ መኖር አይችልም። ወይዘሮ አስካለ የሟች ባላቸዉ የጡረታ ገንዘብ ለእለት ጉርስ ስለማይበቃቸው  ወንድና ሴት በማገናኘት ይተዳደራሉ። ታድያ በየአፍታ ገፃቸውን ይለዋውጣሉ። “ገፃቸዉ የፈገግታ ማስክ ለብሷል። ጓዳ ሲመለሱ ያወልቁታል። ወደ ሳሉን ሲመጡ ይለብሱታል። ሲለብሱ ሲያወልቁ ሊውሉ ነዉ ” መርሶ ያለ ማስኮች ሌጣ ግልፅ ገፁን እየወለወለ በመኖሩ ነዉ ከማህበረሰቡ በባይተዋርነት የተነጠለው። እድገቱም፥ ውድቀቱም ሆነ።
“ሜሪ ... የኔን የሌሊት ልብስ እጅጌውን ጠቅልላ ለብሳለች። ስትስቅ እንደገና አማረችኝ። ከአፍታ በኋላ አፈቅራት እንደሆነ ጠየቀችኝ። ማፍቀር ምንም ማለት እንዳልሆነና እማፈቅራት እንደማይመስለኝ ነገርኳት። ያዘነች መሰለኝ። ... የዛን ቀን ምሽት ሜሪ ልታየኝ መጥታ ላገባት ፍላጐት ያለኝ እንደሆነ ጠየቀችኝ። በእኔ በኩል ምንም ልዩነት እንደማያመጣና እሷ ከፈለገች እንደምንጋባ ነገርኳት። አፈቅራት እንደሆን ማወቅም ፈለገች። የቀድሞውን መልሴን ደገምኩላት። ፍቅር ምንም ማለት አይደለም። ...
“ታድያ ለምን ታገባኛለህ?” ስትል በእውነቱ እሷ ከፈለገች እንደምንጋባ ነገር ግን ለውጥ እንደሌለው ደገምኩላት። ... ጋብቻ የዋዛ ፈዛዛ ሳይሆን ታላቅ ቁም ነገር መሆኑን ጦቀመችኝ። “አይደለም” አልኳት። ... ራሷ ታፈቅረኝ እንደሆነ ለማወቅ በመቸገሯ ተገረመች። እኔም ይህንን ላውቅ ምችልበት መንገድ የለኝም። ከሌላ ዝምታ በኋላ ግራ አጋቢ መሆኔን አጉረመረመች። ምናልባትም ለዚህ ይሆናል ያፈቀረችኝ።”
[ገፅ 37፥ 43-44]
መርሶ በጣም ለሚቀርቡት እንኳን እንዳይቀየሙኝ ብሎ የማስመሰል ባህርይ የለውም፤ እውነቱን እስከተናገረ ድረስ ሌላው ለሚጨነቅበት ጉዳይ ደንታ የለውም። የመሰለውን ከማድረግ አያፈገፍግም፤ የማህበረሰቡን መርህ ባለመከተሉ እንደ እንግዳ - እንደ ባይተዋር ይታዘቡታል። ጓደኛው የሚንከባከባትን ፍቅረኛውን ስለተቀያየሙ ክፉኛ ይደበድባታል፤ ወንድሟ ለበቀል ከጓዳኛው ሲጣሉ በአረቡ ላይ እንዳይተኩስ መርሶ ሽጉጡን ቀምቶት ከኪሱ ይሸሽገዋል። ነገር ከረገበ በኋላ ሙቀቱና ፀሀዩ ወብቆት ለመናፈስ፣ መርሶ ብቻውን ከባህር ዳርቻ ሲሄድ ከአረቡ ጋር ይገጣጠማል።
“አረቡ ከተቀመጠበት ሳይነሳ ጩቤውን ወደ እኔ አስተካከለ። ጩቤው ላይ ያረፈው የብርሃን ብልጭታ ልክ ግንባሬን የሚዘነትል ረዥም ሰይፍ አይነት ነበር። በዚያች ቅፅበት ከቅንድቤ ወደ አይነ-ርግቤ ጠብ ያለው ላብ እይታዬን በአንዴ በሙቀትና በብዥታ ሸፈነው። ... የታወቀኝ ቢኖር ግንባሬን እንደሚደፈጥጠዉ ሹል የፀሀይ ጨረር እና በቅጡ የማይታየኝ የሚያበራው የጩቤው ጫፍ ከፊት ለፊቴ እየበረረ ወደ እኔ መምጣቱ ነበር። ...ሁሉመናዬ ተቆጥቶ በእጄ ሽጉጡን ጠበቅ አደረግኩ። ቃታዉ ሲላቀቅ እጄታው ነቀነቀኝ። ... በተጨማሪ አራቴ ተኮስኩ። ጥይቶች ምልክት ሣይተው በማይንቀሳቀሰው ሰዉ አካል ስር ተቀበሩ። የሀዘንን በር አራቴ በፍጥነት እንደማንኳኳት አይነት ነበር።” [ገፅ 59-60]
የማያውቀዉን ግለሰብ በብዥታ ምክንያት ከገደለ በኋላ ለእስር ቤትና ለፍርድ ውሳኔ ሲጋለጥ ይህ ከማህበረሰቡ መርህ አለመግጠሙ - አለመዋሸቱ፥ ኢ-አማኒ መሆኑ፥ የአስተሳሰብ ባይተዋርነቱ - ፈተና ይሆንበታል። በመለወጥ እና በመጐምራት ላይ እያለ ነው ልቦለዱ የሚያበቃው። አንብበነዉ መርሶ ስለሚመስሉና ስለማይመስሉ ግለሰቦች እንድናጤን ይገፋፋናል፤ ራሳችንም “ባይተዋር ነን ወይ?” በማለት እንጠይቃለን። ያው በዕዉቀቱ ስዩም በ ስብስብ ግጥሞቹ” ገፅ 72፣ የባይተዋር ገድል ብሎ እንደተቀኘዉ ነዉ።
በቁም መስተዋት ፊት መቆምህ ሲጨንቅህ
የቁም መስተዋቱ፥ ”ሰውነትህ የታል?” ብሎ ሲጠይቀህ
..........
“መንሳፈፉስ ይቅር፥ መስጠም ያቅተዋል ሰው?”
ሲያሰኝህ እድልህ
ያኔ ይጀምራል፥ የባይተዋር ገድልህ።
የአልበርት ካሙ “ባይተዋሩ”፣ በአማርኛ ተገርቶ የሚያጣጥመዉ ተደራሲ መነፈጉ፥ ለንባብም አንድ የዘበትነት -absurdity- ጠገጉ ነዉ።

Published in ጥበብ
Saturday, 27 December 2014 16:27

ባለ ቆዳ ካልሲው

ድሮ ሰፈሩ እንደዚህ አልነበረም፡፡ ድሮ፤ ከአስር አመት በፊት ሊሆን ይችላል፡፡ እልም ያልን አራዶች ነን የሚሉ ሁሉ የሚያዘወትሩት ስፍራ ነበር፡፡ አሁን አራዳ በሙሉ ተስፋ ቆርጧል፡፡ የአራዳ ልጅ ጊዜ አልፎበታል፡፡ የአዲስ አበባ ልጅ መሆንም የሚያሳፍር የድሮ ዘመን ሰውነት ነፀብራቅ ተደርጐ ተወስዷል፡፡
አራዳ ነን የሚሉ ብዙዎች ተሰደዋል፡፡ ያልተሰደዱት በከፍተኛ ሱስ ተጠምደዋል፡፡ አራዳ  ለመስራትም ሆነ ለመስረቅ አቅም የለውም፡፡ አራድነት በምላስ ይታወቅ ነበር መጀመሪያ ላይ፡፡ ምላስም ግን በመጤዎቹ ተበለጠ፡፡
ድሮ ሰፈሩ እንደዚህ አልነበረም፡፡ ድሮ፤ ከአስር አመት በፊት ሊሆን ይችላል፡፡ እዚሁ ሰፈር ውስጥ ተቀምጠው ሲቅሙ በሚውሉበት አንድ ትንሽ ጫት ቤት ውስጥ አንድ እንግዳ ሰውዬ በሩን ከፍቶ ከእለታት አንድ ቀን ገባ፡፡
የሰፈሩ ነባር የሆኑት መጤን አይወዱም፡፡ አያምኑም፡፡ መጤ ሁሉ ወራሽ ነው የሚመስላቸው፡፡ የሚወረስ ነገር ባይኖራቸውም እንኳን መጤን ይፈራሉ፡፡ መጤ በሙሉ ገጠሬ ነው፡፡ ይሄንንም ጐልማሳ ገና ከመግባቱ ፊት ነሱት፡፡ ጠጋ ብለው ሊያስቀምጡትም አልፈቀዱም፡፡ ጫት ሻጩ ራሱ ከሚያውቀው ሰው በስተቀር ማስተናገድ የሚፈልግ አይደለም፡፡ ጐልማሳው ቢጫው ጄሪካን ላይ ተቀመጠ፡፡
“ምን አይነት?”      
“እነሱ የያዙትን አይነት”
“የምትፈልገውን ሳታውቅ ነው እንዴ ልትቅም የመጣኸው!?”
“ቅሜ አላውቅም…ቅሜ አለማወቄ ወንጀል ነው”
ጫት ቤቱ ውስጥ የተኮለከሉት አድፍጠው እያጠኑት ነው፡፡ ገጠሬ አለማወቁን ማሳወቅ አይፈልግም፡፡ ከድቁናው ቀድሞ ቄስ መምሰል ይፈልጋል፡፡ አጉል አራዳ በመሆን ነው ፋርነቱን በራሱ እጅ የሚያጋልጠው፡፡ ይሄኛው ለምን ራሱን በማጋለጥ እንደጀመረ አልገባቸውም፡፡
“ወንጀል አይደለም…የሚጣፍጠውን ስጠው…የተቀቀለውን ይስጥህ ወይንስ የታጠበውን?” ተስፋ ከቆረጡት አራዶች አንዱ ጠየቀው፡፡
“የትኛው ይሻለኛል?” እያገዙት በመሆኑ ተደስቷል፡፡ አዲስ የቆዳ ጫማ ነው ያደረገው ግን ጫማው ጠቦታል፡፡ የገበሬ እግሩ ጫማውን አፈንድቶ ራሱን ነፃ ለማውጣት እየታገለ ይመስላል፡፡ ካልሲ አላደረገም፡፡ በሱሪው ያልሸፈነው የእግሩ ቆዳ እንደ አውራሪስ ቆዳ ወፍራም እና ግራጫ ነው፡፡
አራዳው ሊያማርጠው ተነሳ፡፡ ከጀንቡ ውስጥ ጫት እያወጣ ገለፃ መስጠት ጀመረ፡፡
“ይኼኛው የሚያዘፍን ነው…ይኼኛው የሚያሳስብ…ይኸውልህ ይሄ ደግሞ ፍቅር የሚያስይዝ ጫት ነው…ፎቅ እና መኪና የምትፈልግ ከሆነ ደግሞ እቺኛዋን ቃም…”
“የሚያዘፍነውን ስጠኝ - ዘፈን እወዳለሁ”
“ዝህ!” ትልቁን እስር ሰጠው፡፡
የተሰጠውን ይዞ ቀረ፡፡ አራዳው ተመልሶ ተቀመጠ፡፡ በአራድነት የሚበልጠውን በማግኘቱ ደስ ብሎታል፡፡ ግን የተበለጠ መስሎ ለመብለጥ እንደመጣ አውቋል፡፡ ባላወቀ ሙድ መሀላቸው ሊገባ ነው፡፡
የተሰጠውን እስር እንደያዘ ቀረ፡፡ ወደ አራዶቹ ተመለከተ፡፡ እነሱ እንደሚያደርጉት ጫቱን ከፊት ለፊቱ አስቀመጠ፡፡ የጫት እግር መዘው ሲያወጡ አወጣ፡፡ ቀንበጥ ቀንበጡን ሲቀነጥሱ እሱም በጠሰ፡፡ ሲጐርሱ ጐረሰ፡፡በፊቱ ላይ በሚያሳየው ገፅታ ጫቱ በጣም እንደመረረው ያስታውቃል፡፡ ኮካ ይምጣልህ? ተባለ፡፡
አዎ እንደማለት ተወዛወዘ፡፡ ኮካው ሲመጣ በአንድ ትንፋሽ ግጥም አድርጐ ጨረሰወ፡፡ “ጨምርልኝ” አለው ባለ ጫቱን፡፡ የትንሿ ጫት ቤት ብዙ ጭንቅላቶች በጐልማሳው ላይ ተነጣጥረዋል፡፡ ሁለተኛ ኮካ ተከፈተለት፡፡
ቅድም ጫት ያማረጠው አራዳ “ማንም አይጠጣብህም እኮ ቀስ ብለህ ተጐንጭ” አለው፡፡ ጐልማሳው እሺ አለ፡፡
ትንሽ ሲያመነዥግ ከቆየ በኋላ፤
“ልዋጠው ወይንስ ልትፋው?” አለው ለመካሪው አራዳ
“ከዋጥከው የሆድ ቁርጠት ይይዘሃል…ከተፋኸው ደግሞ የሉሉ ትከፍላለህ” አለው ያኛው ቀልጠፍ ብሎ፡፡
ጐልማሳው ማመንዠጉን ቀጠለ፡፡ ኮካውን ቀስ ብሎ ጠጣ፡፡ የጐረሰውን ጫት ሳይተፋም ሳይውጥም ማኘኩን ገፋበት፡፡
ሬዲዮው ከፍ ተደረገ፡፡ የአራዶቹ ሳቅ እና ቀልድ እሱ ላይ መሆኑ አልተሰማውም ወይንም አልገባውም፡፡ አንድ ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተሰጠውን ጫት ግጦ ጨረሰው፡፡ ሲውጥም ሆነ ሲተፋ አልታየም፡፡ አይኑ ፈጠጠ፡፡ የት እንዳለ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ እጁን አሻሸ፡፡
“አሁን በጣም ደስ አለኝ” አለ፡፡ አራዶቹ “እንኳን ደስ ያለህ” አሉት፡፡ “ይድፋህ” ከማለት በተስተካከለ ቅላፄ፡፡
“እስክስታ ልውረድ?” ብሎ አስፈቀዳቸው፡፡ ውረድ አሉት፡፡ ተነስቶ በጠባቧ ጫት ቤት ውስጥ እየተሽከረከረ እስክስታ መታ፡፡ ጉንጩ ውስጥ የያዘው ተክዚና ፊቱ በየትኛው ጐን እንዳለ ያምታታል፡፡ እስክስታ ሲወርድ አጨበጨቡለት፡፡ ሲጨርስ ሌላ ዘፈን ጀመረ፡፡ ልቀጥል? ብሎ አስፈቀዳቸው፡፡ ቀጥል አሉት፡፡ ላቡ ጠብ እስኪል ትከሻውን ሰበቀ፡፡
ጫት ሻጩ ተቆጣ፡፡ “ይሄ ጭፈራ ቤት…ናይት ክለብ አይደለም! አርፈህ ቁጭ በል ወይ ውጣ!” አለው፡፡ እሺ ብሎ ተቀመጠ፡፡
አራዶቹ ለሻጩ አስረዱት “ጫት ቅሞ ስለማያውቅ ምርቃና እንደ ስካር መስሎት ነው…ተጠጥቶ እንደሚደነሰው ተቅሞ የሚደነስ መስሎት ነው” አሉት፡፡ እነሱን እንዳሳቃቸው እሱን አላሳቀውም፡፡     
ተቀመጠ፤ ላቡን እየጠረገ፡፡ ዘፈኑ ተቀነሰ፡፡ “ሌላ ጫት ይጨመርልኝ” አለ፡፡
“ቅድም ያደቀቅሕውን መጀመሪያ ክፈል” ተባለ፡፡ የሱሪ ኪሱ ውስጥ ሲገባ ብዙ መቶ ብሮች ይዞ ወጣ፡፡ ለራሱም ለሌሎችም አዘዘ፡፡ አንድ ዙርባ ጫትን እንደ አንድ ጠርሙስ ቢራ ነው የቆጠረው፡፡ ሩብ ጫት የጠረረበት የሰፈር አውደልዳይ፤ አንድ ሙሉ ጫት ሲሰጠው እየተቀበለ ጥጉን ያዘ፡፡
“በጣም ደስብሎኛል” አላቸው ጐልማሳው
“ለምን?” አሉት፡፡
“ሎተሪ ስለደረሰኝ” አላቸው፡፡
“ስንት ደረሰህ?” ሎተሪውን አውጥቶ አሳያቸው፡፡ ሎተሪ የደረሰው ሰው በዝቅተኛ ገንዘብ (በሁለት ሺ ብር) የአንድ ማሊዮን ብሩን ሎተሪ እጣ እንደሸጠለት ነገራቸው፡፡
“እንኳን ደስ አለህ” ብለው ጨበጡት…የደስ ደስ ሁሉንም ሊጋብዝ እንደሚፈልግ ነገራቸው፡፡ አብሽር አሉት፡፡
በቃመ ቁጥር ደስታው እየናረ በመምጣቱ፣ ምን ማድረግ እንዳለበት ጨነቀው፡፡
“ጨመቅ አድርገህ ቃም፤ ውሀም አብዝተህ ጠጣ” አሉት፡፡
“አብዝቼ ካልጠጣሁስ?”
“አልወጣ ይልህና…በኋላ በቪኖ መክፈቻ ካልሆነ ሰገራህ አይወጣም”
ሳቁበት፡፡ ሳቀላቸው፡፡
ካልሲ ከሚያዞር ሱቅ በደረቴ በጫት ቤቱ መስኮት ነጭ ካልሲ ገዛ፡፡ “ካልሲ ምን ያደርግልሃል… አንተ እኮ ምርጡን ካልሲ ነው የለበስከው”
“እውነታችሁን ነው…አዲስ ጫማ በአዲስ ካልሲ ካልተደረገ ይሸታል ብለውኝ እኮ ነው”
“የሚናገሩትን አያውቁም ይቅር በላቸው…የአንተ ካልሲ በአለም ዙሪያ ተፈልጐ አይገኝም፡፡ አንተ እኮ የማያረጅ፣ የማይሰፋ፣ የማይቆሽሽ ካልሲ ነው ያደረግኸው…የጨርቅ ካልሲ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ አንተ የሌዘር ካልሲ ነው ያደረከው” ጐንበስ ብሎ እግሩን አይቶ፣ በተፈጥሮ ካልሲው ተኩራራ፡፡
“ይልቅስ በነፃነት መደነስ ከፈለክ፣ በባንድ የሚቃምበት ቤት ስላለ እዛ ይዘንህ እንሂድ
…በብራስ ኦርኬስትራ ሌሊቱን ሙሉ እየተቃመ የሚጨፈርበት ቤት ነው”
“አሁኑኑ እንሂድ” ብሎ ተፈናጥሮ ተነሳ፡፡
“ቆይ ተረጋጋ እንጂ በባንድ የሚቃምበት ቤት ሌሊት ነው የሚከፈተው… በዚያ ላይ ሴቶች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ሴቶቹ እንዲወዱህ ፍቅር የሚያሲዘውን ጫት እየቃምክ ቆይ፡፡ ፍቅር የሚያሲዘውን ጫት ስትጨርስ ፎቅና መኪና የሚያስገዛውንም ብትሞክር አይጐዳህም…”
“ልክ ነው…መኪና መግዛት አለብኝ፡፡ የሎተሪውን ብር ተቀብዬ ስመለስ ሚስትም ገዝቼ ወደ ሀገሬ ብገባ ማለፊያ ነው”
“ሴቶች ደግሞ መኪና ይወዳሉ ታውቃለህ አይደል…የእኛ የወንዶች አይን የተሰራው ከሴቶች ዳሌ እንደሆነው ሁሉ…የሴቶች አይን ደግሞ የተሰራው ከመኪና እቃ ነው…ለዚህ ነው መኪና ሲያልፍ አይናቸውን መንቀል የማይችሉት…እኛም ወንዶች ሴቶች ሲያልፉ አይናችንን ከዳሌያቸው ላይ መንቀል አንችልም አይደል?”
“ልክ ነህ…በደንብ ነው ነገሮችን የገለፅክልኝ…ስለዚህ መኪና መግዛት ይቀድማል ማለት ነው?”
“እንደ ምርጫህ ነው…በባንድ የሚቃምበት ቤት መዝናናት…ወይንስ ሴቶችን ማዝናናት ወይንስ መኪና?”
“መኪና ስንት ነው ዋጋው? አንድ ሚሊዮን ብር ነው የደረሰኝ”
“አንድ ሚሊዮን ብር … አንድ ሚሊዮን መኪና መግዛት ይችል ነበር…ችግሩ ጐማው ነው፡፡ መኪና ያለ ጐማ አይሽከረከርም… ጐማ በጣም ውድ ነው፡፡ ጐማው ለምን መሰለህ ውድ የሆነው? ባዝሊን ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ ባዝሊን ሀገር ውስጥ አይመረትም፤ የማመጣው ከአውስትራሊያ ብቻ ነው፡፡ ባዝሊን ካልተቀባ ጐማ አይሽከረከርም፤ ስለዚህ ዋናው ጉዳይ መኪና ሳይሆን ባዝሊን ነው…” አለው አራዳው፡፡
“ስለዚህ ምን እንዳደርግ ትመክረኛለህ?” አለ ባለ ሌዘር ካልሲው፡፡
“እኔ እንዳጋጣሚ ባዝሊን በርካሽ ዋጋ የሚሸጥ ሰው አውቃለሁ፡፡ ሰውየው ሀገር ጥሎ ሊሄድ ስለሆነ የባዝሊን በርሜሎቹን የሚገዛው ሰው ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ በደንብ አስብበትና ባዝሊን ንግዱን ተረክቤ ልስራ የምትል ከሆነም ትችላለህ…አይ ተዝናንቼ ወደ ሀገሬ የሎተሪ ሽልማቴን ይዤ ልግባ ካልክም ያንተ ምርጫ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን በደንብ አስቦ ለመወሰን እንዲረዳህ…ከዚህ ቤት ከመውጣትህ በፊት የማሰላሰያ ጫቱን አንተም እኔም ብንቅም ጥሩ ነው…ከዛ ማታ ተያይዘን በባንድ ወደሚቃምበት ቤት እንሄዳለን”
“በጣም ነው ደስ ያለኝ ዛሬ…ስለተዋወቅኋችሁ ደስ ብሎኛል…ሁላችሁንም፡፡ በተለይ አንተ ስምህ ማነው?”
“ስሜን አስይዘህ ትበደርበታለህ አልነግርህም” ሌሎቹ ሳቁ፡፡
“ስምህ ራሱ የገንዘብ እውቀት ባለው ሰው የወጣ እንደሆነ ያስታውቃል…አቶ አስይዘህ ትበደርበታለህ…የአያትህ ስምስ?”
“ፊት አውራሪ አልነግርህም…የአንተስ?”
“የእኔ ኮንስታብል ዘረ ያዕቆብ ነው…በባንድ ስለሚጨፈርበት ጫት ቤት እዚያው ፖሊስ ጣቢያ ትነግሩኛላችሁ…መኪና ይምጣና አንድ ላይ እንሄዳለን…” መታወቂያውን አውጥቶ አሳያቸው፡፡ እውነትም ፖሊስ ነው፡፡
 ፖሊስ ሲሆን ታዲያ ድንገት ቁጡ ሆነ፡፡ ፊቱ ጠበብ፣ ጫማው ሰፋ ያለ መሰለ፡፡
 

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 27 December 2014 16:26

የእብዶች ሸንጎ

    አፈጉባኤው የጫት ገረዊናውን እያነሳ የንግግር ማድረጊያውን ጉብታ መሬት እየደጋገመ ያጎነዋል። ለፓርላማው አባላቱ  ስለ ስብሰባው ፍሬ ነገር ሹክ ለማለት በእጅጉ እየተጣደፈ ነው። ጉሮሮውን በልቅላቂ የሀይላንድ ውሀ እያጠበ የመክፈቻውን ንግግር ጀመረ፤
“ከጊዜ ግሳንግስ ውስጥ ይህቺን ቅጽበት ብቻ ተውሰን እብዳታችንን ፊት መንሳት እንጀምራለን። ከእብደታችን ጋር ለመፋታት ስንዳዳ ማንገራገሩ ሊከፋብን ይችል ይሆናል፡፡ ማንገራገሩ ግን ግፋ ቢል አፍታን ነው የሚሻገረው። ጉባኤውን ከእብድ ጉባኤነት ልንታደገው ይገባል፤ ከተተመነለት የሰዓት ኮታ ውጭ ውልፊት የሚል ተሰብሳቢ ካለ ጫንቃችን ሊሸከመው ዝግጁ አይደለም።” አለ ጭንቅላቷ ከጣቱ መሀል የደረሰችን ኒያላ ሲጋራን በፍቅር እየማገ፡፡
ስብሰባው ከጅመሩ ያልተዋጠለት እብድ፤ የንግግሩን ቅድሚያ በጉልበት ወሰደ፤፡፡ በሱስ ካበደው ወገን ነው። ይህ ወገን የሽንጎውን ሲሶ ክፍል ይሸፍናል። እብዱ የያዘውን የብረት ቁርጥራጭ እያንኳኳ ልፍለፋውን ተያያዘው፤
“ገደብ፣ ክልከላህን ፊት ንሳና ፍሬነገርህን ሹክ በለን። ቆይ … ቆይ … ዘንግቼው … እንደውም ... ስብሰባውን ለምን በህሊና ጸሎት አንጀምረውም……”
“የህሊና ጸሎት ከእዚህ ምን ዶለው?” አፈጉባኤው በሀይለ ቃል እያበሻቀጠ የመልስ ምት ሰጠው
“ክቡር-አፈጉባኤ…….ይህንን ማዕረግ ተሸክመህ ለህሊና ጸሎት….እንግዳ መሆንህ …ደንቆኛል፤ ለማንኛውም… የአብራካችን ክፋይ የሆኑ ...በተከርቸም አባዜ የሚናውዙ… የእግረ-ሙቅ…ሲሳዮችን…. ለማሰብ ሁላችንም ከተንጋለልንበት እንነሳ” አለ በስሜት ወዲህ ወዲያ እየተወዛወዘ፡፡
ከተንጋለለበት የተነሳ እብድ ግን ማየት አልቻለም። በተሰብሳቢው ልግምተኝነት የተነሳ እብደቱ ሊያገረሽበት ከአፋፍ ላይ ደርሶ ተናነቀው ፤ከውስጥ ሱሪው ውስጥ የተጎመደች ሲጋራውን አውጥቶ አየር ላይ ለመለኮስ ይጣጣር ጀመረ፤ መለፍለፉን ሳያቋርጥ፡፡
“እናንተ ብሎ እብድ ፤ይሄኔ ለቀፈታችሁ ውትወታ ጥሞና ስጡ ቢሏችሁ በአደባባይ ላይ ትበዙ ነበር፤ ዝንተአለም ጎብጣችሁ ብታዘግሙ ግድ አይሰጠኝም፤ እኔ እንደሁ..አንድ ለራሴ አላንስም” በንዴት ስብሰባውን እረግጦ ተፈተለከ፤ግድ ያለው እብድ አልነበረም።
የጉባኤው አየር ሊረግብ አልቻለም። አየሩም የተሰብሳቢው መንፈስ ተጋብቶበት በላይ በላይ እያበደ ነው። የሚንሸዋሸው የፌስታል ድምጽ ከርቀት እየሰነጠቀ መጣ። የሚታይ ሰው  የለም። ድምጹ ግን እየቀረበ ነው። ትንሽ ሰከንድ ፈቀቅ እንዳለ ከድምጹ አቅጣጫ የተበጠሰ ኤርጌንዶ ነጠላ ጫማ ውስጥ የተቸረቸፉ የእግር ጣቶች ብቅ አሉ። ለጥቆ ቀርፋፋ ቀውላላ ሰው እንደ ጅብራ ተገተረ። ጅብራው በቀጣጠለው የላዉንደሪ ላስቲክ ውስጥ የጫት ገረባ፣’የመከኑ ሲጋራዎችና ክዳን አልባ የሀይላንድ ላስቲኮችን ሰብስቧል። ያዘለውን ኮተት ለፓርላማው ታዳሚዎች ከፈተላቸው። በሙሉ  ሰፈሩበት። ከቅራቅንቦው ብፌ የየፍላጎታቸውን ለመቃረም እጃቸውን ሰደዱ። ጅብራው በፌስታሉ ውስጥ ያሉት ኮተቶች የእብዶቹ ሲሳይ ሲሆኑ ደንታ ባይሰጠውም፣ በማሳረጊያው ላይ ግን  ለአንድ ነገር ስስት ያዘው:: የገነፈለ ብዕር ነበር፡፡ ብዕሩን ሊያጋፍፍ እጁን የዘረጋውን እብድ አፈፍ አደረገው፡፡ ጅብራው ለወረቀትና ለብዕር ነክ ነገሮች በሚሰጠው ክብር ከዘመኑ እብዶች ለየት ይላል፡፡ “ምሁር እብድ ነኝ” ብሎ ስለሚያስብ ሌሎችን በንቀት ነው  የሚመለከተው። በፈረንጅ አፍ ሲያወራ አላፊ አግዳሚው ሳይወድ በግዱ ቀልቡን ሰብስቦ ጆሮውን ያውሰዋል። ዛሬ እነዚህን የዘመኑ እብዶች ምን እንዳሰባሰባቸው ግር ተሰኝቷል። የገነፈለውን ብዕር ከደረቱ ላይ እንደለጠፈ ባለበት ተቸንክሮ ሁኔታውን ለመከታተል ወሰነ።
ብቸኛዋ የሴት እብድ ተወካይ እጇ ላይ የሚያንኮራፋ ጨቅላ እንደታቀፈች ብድግ አለች። የተኛውን ጨቅላ ላለመቀስቀስ በጣም በዝግታ ታንሾካሹካለች። ለጨቅላዋ ምቾት እብደቷም አንዳንዴ ታጋሽ ይሆናል። የተነሳችበትን ፍሬ ሀሳብ በሹክሹክታ ድምጽ እየሰነዘረች ነው። ንግግሯ ለእብዶቹ ሊሰማቸው ስላልቻለ ባለ በሌለ ሀይላቸው  ጆሯቸውን አስግገው ወደ ሹክሹክታው አዘነበሉ።
“የጾታ እኩልነት ለምን በእብድ አለም አይሰራም። ጤነኛ ሆናችሁ የተጠናወታችሁ ንቀት አብዳችሁ እንኳ አይለቃችሁም፤ እብደት ማለት የጾታና የዘር  አጥር የሌለው ልቅና ዝርግ ህይወት ነው፤ እናንተ እብድ አይደላችሁም። አውቆ አበድ ናችሁ። ማበዳችሁን ያወቃችሁ። ለእብደታችሁ ጤነኞች እውቅና እንዲሰጧችሁ የምትንገበገቡ የታይታ እብዶች። ጉስቁላናችሁን እንደ ቀብድ አሲዛችሁ ትርፍ ለማጋበዝ የምትታትሩ ከንቱዎች፤ከንፈር እንዲመጠጥላችሁ ላይ ታች የምትሉ አስመሳይ ቀውሶች!” ብላ በበለዘ ሻሿ ፊቷን አበሰችው፡፡
ቀውሶች የሚለውን ቃል ስታወጣ  እልህ ቢጤ ስለተናነቃት፣ ድምጿ ከተኛው ጨቅላ ጆሮ ሰርስሮ ገባ። ጨቅላው በጩኸቱ አካባቢውን እውነተኛ የእብድ ሰፈር አስመሰለው። እብዷ ወዲያው ወደ ቀልቧ ተሰብስባ፣ ግቷን ለጨቅላው ስታቀብልና ጩኸቱ ሲረግብ አንድ ሆነ።
ምሁሩ እብድ የሴትየዋን ተሳልቆ በጥሞና ተከታትሎታል።
“We need to revolutionize our thinking behavior” አለ በሚታወቅበት የእንግሊዘኛ ችሎታው። እብዶቹ በሙሉ የተናገረውን ወደ ሀበሻ አፍ እንዲለውጥላቸው በአንድ ላይ ተንጫጩበት፤ ግድ አልሰጠውም…..ጉራማይሌ እያደረገ ንግግሩን ቀጠለ፤
“ቆይ እናንተን ከእብድ ማህበረሰብ ጋር እንድትቀላቀሉ የፈቀዳለችሁ ማን ነው? የእኛ ትውልድ እብድ መለመላውን ሆኖ በእንግሊዝ አፍ እየተቀኘ የሚንጎራደድ…ወደል ነበር፤ ትንሽ እንደተጓዘ በጤነኞች አጀብ ይደረግለታል። It was so majestic………….፡፡
የእናንተ አጀብ የገዛ ጥላችሁ ነው። ቆይ እኔ የምለው ወይ በእንግሊዝ አፍ አትቀኙ፣ ወይ በሀበሻ አፍ አትቀኙ። ሁለመናችሁ የተሸበበ ልጉም ፍጡሮች! እኔ የማዝነው ያ ወርቃማ የእብድ ማህበረሰብ አልቆ እኔ ብቻ በመቅረቴ ነው። ትውልዳችንን ከመጥፋት የሚታደገው ማን ነው? በቃ የእብድ ማህበረሰብ ማለት ይህ ነው?”  ስቅስቅ እያለ ማንባት ጀመረ፡፡ የእርሱን ሀዘን የተጋሩ ሌሎች እብዶች አብረውት ተነፋረቁ፡፡
አፈጉባኤው ጸጥታ ለማስጠበቅ የጫት ገረወይናውን አንስቶ ሊደበድብ እጁን ሰደደ። ገረወይናው  የለም። ዞር ሲል ወይጦ ከሚባለው እብድ ጋር አይን ለአይን ተላተመ፡፡ ገረወይናው የወይጦ ካራ ሲሳይ ሆኗል። ብሽቀቱን ለመሸሸግ እየሞከረ ካጠገቡ ተንጋላ በተቀመጠችው ቁራጭ የሀይላንድ እቃ  ጉብታውን መሬት ልቡ እስኪጠፋ እየደጋገመ ደበደበው።
“ጸጥታ! ጸጥታ! ለመነፋረቅ አይደለም የተሰበሰብነው። መላ ልናወጣ ልናወርድ እንጂ። ጸጥታ…….ጸጥታ!” ሀይላንዷ እስክትነደል ድረስ ጉብታውን መቀጥቀጡን አላቆመም። እብዶቹ አፈጉባኤውን ብዙ ሳይንገራግሩት ቀና ምላሽ ሰጡት።
ቃለጉባኤ እንዲይዝ የታዘዘው እብድ የጨበጠው ብዕር አልፅፍ ስላለው ቅዝዝ እንዳለ በቀፎው መሬቱን ይቆረቁራል። ድንገት መሬት መቁርቆርን ገታ አደረገና እምር ብሎ ተነሳ። ሽቅብ ወደ ሰማይ አንጋጠጠ። ሁሉም እብድ በአይኑ ተከተለው። እብዱ አይኑን ከአንድ ነገር ጋር እየተከተለ ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ ያንከራትታል። አይኑ የሚንከራተተው በአካባቢው ቅኝት በሚያደርግ አሞራ ላይ ነው። አሞራው ያንዣብባል። አንዴ ቁልቁል እንደ ሚግ አውሮፕላን  ክንፉን ጨምቆ ይወረወርና ይመለሳል፤ በድጋሚ ክንፉን ጨምቆ ይወረወራል። ምንም የለም። ይመለሳል። መወርወር መመለስ። መወርወር መመለስ። ለሀምሳ ጊዜ ተመላለሰ። በሀምሳኛው ላይ አንዲት ግልገል አይጠ መጎጥ በጥፍሩ ጨምድዶ፣ በአሸናፊነት አየሩን እየገመሰ ከአይን ተሰወረ።
 ሁሉም እብድ  ትእይንቱን ከጅምሩ አንስቶ ነፍዞ እየተከታተለው ነበር።
“አሁን ከእዚህ ትዕይንት ለእብድ ማህበረሰብ ምን የሚፈይድ ነገር ተማርን?” አለ ቃለጉባኤ ፀሐፊው፡፡“እብድና  ብኩን አሞራ አንድ ናቸው። አሞራውስ ሀምሳ ጊዜ ተንከራቶ አንድ አግኝቷል፤ እብድ ግን ለእዚህ አልታደለም። ሀምሳ ጊዜ ተመኝቶ ሀምሳውንም የሚያጣ፤ ሀምሳ ጊዜ ጠይቆ ሀምሳ ጊዜ የሚነፈግ፤ ሀምሳ ጊዜ አንብቶ አንድ ጊዜም የማይፈግግ ብኩን አሞራ ነው፤ ስለዚህ ቢያንስ ከእዚህ አሞራ እንማር፤ ሀምሳ ጊዜ ለፍተን አንድ እንቃርም፤”
“ምንድን ነው የምንቃርመው?” አለ አፈጉባኤው ድንገት አቋርጦት
“እብደታችንን ነዋ፤ እውነተኛ እብድ እንሁን፤ እስካሁን እብድ ለመሆን ተንከራተናል፤ በእርግጥ ቆሽሸናል፤ አዳፋ ተከናንበናል፤ ከገንዳ ውስጥ ፍርፋሪ እየለቀምን እድሜያችንን ቀጥለናል፤ ግን አሁንም ከትክክለኛው እብደታችን ጋር በአይነ ስጋ አልተያየንም። እውነተኛው እብደታችን ከእቅፋችን ውስጥ የሚገባው እንዲህ በረባው ባልረባው ብርክ የሚይዘው ልባችን መጀገን ሲጀምር ነው።
እስቲ የትኛው እብድ ነው ጤነኞች የሚወረውሩበትን  ፍላጻ  ለመመከት ደረቱን በጀግንነት ገልብጦ የሚሰጠው፤ የትኛው እብድ ነው እጁን ወደ የሚንቀለቀል እሳት የሚልከው፤ የትኛው እብድ ነው አንድዬ ብርቅዬ ህይወቱን እየሳቀ የሚሸኘው ፤ አያችሁ እኛ እብዶች አይደለንም፤ ምስኪን ጤነኞች እንጂ፤ ምስኪን ጤነኛ ደግሞ ከእብድ እግር ጋር አይተካከልም? እንዴት ይተካከላል…” ጠየቀ ተሰብሳቢውን፡፡የጉባኤውን መንፈስ ለማረጋጋት ሌላ እብድ ከተቀመጠበት ተነሳ። በመስተፋቅር ካበደው የፓርላማው ወገን ነው። አናቱ ላይ ብጭቅጫቂ ዳንቴል አጥልቋል፤ አንገቱ ላይ  ሻሽ ጠምጥሟል፤ የደረቱን እኩሌታ በእሳት በተበላ  ጡት መያዣ ሸፍኖታል፤ ሚጢጢዬ ጠጠር ድንጋይን እንደ ክሬን እየተጎተተ ከመሬት በማንሳት በጩኸት መናገሩን ቀጠለ፤ “ለምንድን ነው ግን ወደ ራሳችን የማንመለከተው፤ ድሮ ድሮ እብድ ሲባል የጠገበ ዱላ ይዞ የሚንጎራደድ ወጠምሻ ነበር፤ የእብድ ስም ሲነሳ የማይሸበር ጤነኛ አልነበረም፤ እንደውም እስከነተረቱ….“እብድ የተናገረው መሬት አያርፍም” ይባላል፡፡
ፍልስፍናው ዝብርቅርቅ፣ ወሬው የጤነኞችን የማሰብ አቅም የሚፈታተን ነበር፤ ዛሬስ? ዛሬማ ተንቀናል፤ እስቲ ተመልከቱን …..ለአይን የሚያጠግብ እብድ ከእዚህ ውስጥ ይፈለግ ቢባል አይገኝም፤ በአካልም በመንፈስም ደቀናል። አንደበታችን ዲዳ፤ አካላችን ለንቋሳ ሆኗል። እጃችን በዱላ ፋንታ የተጣለ ሀይላንድ መለቃቀም ከጀመረ ሰነባብቷል።
 ፍልስፍናችን በዝምታ ተቀይሯል። የድሮ እብደታችንን ማምጣት ለነገ የምንለው ስራ መሆን የለበትም።”ቀኝ እጁን ወደ ላይ እየሰቀለ መፈክር ማሰማት ጀመረ፤ “እብደታችን እንደ ድሮ ይሆናል! እብደታችን እንደ ድሮ ይሆናል!” አስደንጋጭ መፈክር ከሞቀ ጭብጨባ ጋር አጀበው። ጭብጨባውን ሰምቶ ይሁን ድንገት… ስጋ የጠገበ መለዮ ለባሽ ዱላውን አክሮባት እያሰራ ከርቀት ወደ ስብሰባው ሲመጣ ታየ፡፡ ሁሉም ተሰብሳቢ በፍርሀት ልቡ ይርድ ጀመረ።
አፈጉባኤው በእዚህ ጊዜ፤
“አንድ ጊዜ ……አንድ ጊዜ፤ አሁን ጤነኛውን ከእብድ፣ ፍሬውን ከገለባ መለየት ቸለናል፡፡ በአንድ መለዮ ለባሽ  እንዲህ የሚርድ ልብ ካለን፣ ጤነኛ የመሆናችን ፋይዳው ምኑ ላይ ነው። …ኸረ.. እብደት በስንት ጣዕሙ….. በሉ ወደ የሚያዋጣን እብደታችን እንመለስ” ብሎ በንዴት ስብሰባውን በተነው።

Published in ጥበብ
Saturday, 27 December 2014 16:25

ዛሬም ይዞረኛል

ሄደ … አለፈ ብዬ ትንሽ ፋታ ሳገኝ፣
የተጫነኝ ችግር የጠፋ ሲመስለኝ፣
ተመልሶ መጥቶ ጎንተል ያደርገኛል፣
የራቀ ሲመስለኝ ዳግም ይቀርበኛል፣
ከጋለው ሊጥደኝ መልሶ ይዞረኛል፡፡
እኔ ቀርቤው ነው? ወይ እሱ እየመጣ፣
የማንለያየው - የማንተጣጣ፡፡
አንዴ እየራቀ፣ ዳግም እየመጣ …
        ይሽከረከረኛል፣
ቁራኛዬ ሆኖ አልለቅህም ብሎ …
        ያንዣብብብኛል፡፡
ከዚህ ችግር ዕዳ - ከእንቶ ፈንቶ ጣጣ፣
ሊያድነኝ ከሁሉም ከማጡ ሊያወጣ፣
ዳግም ወደ መሬት ክርስቶስ አይመጣ፣
ታዲያ እንዴት ልሁነው?
እንዲሁ እንዳለሁ ፍግም ልበለው!?
        … ኧረ አሳዝናለሁ፣
        … አፈር እከብዳለሁ፡፡
ይህ መንገራገጩ ጠቅልሎ አልሄድ ያለው፣
እንዴት ቢያፈቅረኝ ነው ከኔ የማይለየው!?
ፊትም፣ አምና፣ ዛሬ አልተውህ ብሎኛል፣
ነገሩ ምንድነው? - ዛሬም ይዞረኛል፡፡

ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
ታህሣሥ 2007 ዓ.ም

Published in የግጥም ጥግ
Saturday, 27 December 2014 16:21

አማርኛ የራሱ ፊደል አለውን?

በክፍል ፩
 ፅሑፌ፤ የአማርኛ ፊደሎች (ሆሄያት) በዝተዋልና ይቀነሱ (ይሻሻሉ) በሚሉ የቋንቋ ምሁራን የተሰነዘሩትንና እየተሰነዘሩም ያሉትን ሀሳቦች ከብዙው በጣም በጥቂቱ እንደገለጽኩ ይታወሳል፡፡
 በማጠናቀቂያዬም “ለመኾኑ አማርኛ የራሱ የኾነ ብቸኛ ፊደል (የፊደል ገበታ) አለውን?” የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ እናም በቀጠሮዬ መሰረት ይኸው የያዝኩትን ይዤ ብቅ ብያለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡
“ነገርን ነገር ያነሳዋል” ይባል የለ፡፡ እናም ወደ ዋናው ጉዳይ ከመሔዴ በፊት “ፊደል” የሚለውን ቃል በተመለከተ አንድ ሐሳብ ላነሣ ፈለግሁ፡፡ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ፊደል የሚለው ቃል ሆሄ ከሚለው ቃል ጋር በተምታታ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሲውሉ በማየቴ ነው፡፡
በእርግጥ እንደ ልምድ ሆኖ ይመስላል ሆሄ በማለት ፈንታ ፊደል እያልን ስንጠቀም ቆይተናል፤ እየተጠቀምንም እንገኛለን፡፡ ያም ሆኖ ግን መግባባታችን አልቀረም፡፡ “ቋንቋ መግባቢያ አይደል እንዴ! እኛ ከተግባባንበት ቢባል ምን ችግር አለው?” የምትሉኝ ትኖሩ ይሆናል፡፡ ተሳስታችኋል ከሚል ድምዳሜ ፈጥኜ አልገባም፡፡
ይሁን እንጂ በሥነ ጽሑፍ ውስጥ አንድ ቃል ሊገልጸው የሚፈልገውን ነገር በትክክል ሊያስረዳ ካልቻለ ጸያፍ ከመሆን አያልፍም፡፡ “እንጀራ እየጋገርሁ ነው” ለማለት “ምጣድ እየጋገርሁ ነው፡፡” አይነት ይሆናል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ስለ ፊደልና ሆሄ ልዩነትና አጠቃቀም ብንሳሳት ወይም ባናውቅ አይፈረድብንም፡፡ ምክንያቱም ስለ ሁለቱ ቃላት ግልጽ በሆነ መንገድ የሚያብራራ መዝገበ ቃላት አልተዘጋጀምና፡፡ አንዳንዶቹ መዛግብተ ቃላትማ ፊደልን ጠቅሰው ሆሄ የሚለውን ዘልለውት እናገኛቸዋለን፡፡
ወደ እንግሊዝኛው መዝገበ ቃላት መለስ ብለን እስቲ “አልፋቤት” እና “ሌተር” የሚሉትን ቃላት ትርጉም እንመልከት፡፡
Alphabet:  The set of letters used in writing any language, esp. when arranged in order, eg. Greek alphabet, Russian alphabet. Letter: any of the sign in writing or printing that represent a speech sound. “B is a capital letter “b” is a small letter.   (Longman Dictionary of Cont. English)
እዚህ ላይ እንደምንመለከተው በእንግሊዝኛው መዝገበ ቃላት alphabet (ፊደል) እና letter (ሆሄ) ግልጽ ትርጉም ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ ወደ አገራችን ስንመጣ፣ ካሉት መዛግብተ ቃላት መካከል ቀረብ ያለ አተረጓጎም የያዘው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታተመው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር አማርኛ መዝገበ ቃላት ፊደል የሚለውን ቃል፡-
“ፊደል፡- ንግግርን በጽሑፍ ለማስፈር የሚያስችልና ድምጽን ወክሎ የሚቆም ምልክት (ለምሳሌ ሀ፣ ለ …) በማለት ተርጎሞታል፡፡ ሆሄ ለሚለው ቃል ደግሞ “ሆሄ (ብዙ ሆህያት) ስ. ከግእዝ እስከ ሳብዕ (ለምሳሌ ከሀ-ሆ ወይም ከሀ-ፐ) ያለው የፊደላት ስምና መልክ ወይም ቅርፅ” የሚል ትርጉም ሰጥቶታል፡፡
ለማንኛውም ፊደል ንግግርን በጽሑፍ ለማስፈር የሚያስችሉና ድምፅን ወክለው የሚቆሙ ምልክቶች (ሆሄያት) ስብስብ ሲሆን ሆሄ ግን ለአንድ ድምፅ የሚወከል ምልክት ነው የሚለውን ትርጉም በመያዝ ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ልመልሳችሁ፡፡
እዚህ ዝርዝር ውስጥ የገባሁት ወደፊት ባለው ጽሑፌ የሁለቱ ቃላት አገባብ አንባቢዎችን ግር እንዳያሰኝ በማሰብ ነው፡፡ እናም “አማርኛ የራሱ የሆነ ፊደል አለውን?” የሚለውን እንመልከት፡፡
አማርኛ የራሱ የሆነ ፊደል አለው ወይም የለውም የሚል ብያኔ ከመስጠታችን በፊት ግን የት መጣነቱን ማየት ወይም ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህንንም ለመረዳት ከኢትዮጵያዊው ፊደል ማለትም ከግዕዝ ታሪካዊ አመጣጥ መነሣቱ ለግንዛቤ ይጠቅማል፡፡
ስለ ግዕዝ ፊደል አመጣጥ ሁለት ዓይነት አመለካከቶች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ እነዚህም ሃይማኖታዊና ሳይንሳዊ አመለካከቶች ናቸው፡፡ የሃይማኖት ሊቃውንት ስለ ፊደል አመጣጥ ሲገልጹ፣ ፊደል ከአዳም ሦስተኛ ትውልድ በሆነው በሄኖስ አማካይነት ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠ ነው፡፡ በልሳን ተውጦና ተሰውሮ የነበረው አካሉ በሰማይ ገበታነት ተጥፎ፣ ተቀርጦ የተገለጠ ነው በማለት፤ (ኩፋሌ 5፥18)ን በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ ፊደሉም ግዕዝ ነው ይላሉ፡፡
የፊደሉም ሆሄያት መደበኛ ቁጥራቸው ከእሁድ እስከ ዐርብ በተፈጠሩት ፍጥረታት ልክ 22 ናቸው፡፡ በእነሱ ላይ ደግሞ በመጥበቅና በመመሳሰል ምክንያት ተደራራቢ ሆሄያት (ሰ፣ኃ፣ዐ፣ፀ) ሲጨመሩ ኻያ ስድስት ይሆናሉ በማለት ይገልጻሉ፡፡
በሳይንሳዊ አመለካከት በኩል የሚቀርበው የግዕዝ ፊደል አመጣጥ ታሪክ ግን ከሃይማኖት ሊቃውንት አባባል የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
እንደ ሳይንሳዊ ጥናት አድራጊ ምሁራን አባባል፤ የሰው ልጅ ፊደልን በሚሊዮኖች ዓመታት የዕድገት ደረጃዎች ለውጡ ቋንቋውን ከሥልጣኔ ዕድገቱ ጋር አብሮ እያራመደ ሲመጣ ያገኘው ውጤቱ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
በዚህም መሰረት አስቀድሞ ሸክላ፣ ቆዳ፣ ብረት፣ እንጨትና የመሳሰሉት ልዩ ልዩ ቅርፃቅርፆችንና ምልክቶችን በመጠቀም መልእክት ለማስተላለፍ ቻለ፡፡ በእነዚህ ሥዕላዊ ምልክቶች (Pictographic Symbols) ከመጠቀም አልፎም ወደ ጽሑፍ ቋንቋ (Writing Language) በቅቷል የሚል ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡
የሳይንሳዊ ጥናት ተመራማሪዎች ከላይ እንደተገለጸው፤ የሰው ልጅ ለንግግሩ ጽሑፋዊ መግለጫ የሆነውን ፊደል መፍጠር እንደቻለ አረጋግጠዋል፡፡ እዚህ ላይ ግን አንድ ልንገነዘበው የሚገባን ነገር ይኖራል፡፡ ሃይማኖታዊም ሆነ ሳይንሳዊ አመለካከት ያላቸው ሁለት ክፍሎች፤ በፊደል ታሪካዊ አመጣጥ ላይ የተለያየ አቀራረብ ቢኖራቸውም በአጠባበቅና በአጠቃቀም በኩል ግን በአብዛኛው አንድነት ያላቸው መኾኑን ልንረዳ ይገባል፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው፤ የሰው ልጅ ፊደልን ከማግኘቱ በፊት ለፊደል መፈልሰፍ መሰረት የሆኑት ሥዕላዊ ምልክቶችን ይጠቀም እንደነበረ ተገንዝበናል፡፡ እነዚህ ሥዕላዊ ምልክቶች የግብፅ ሂሮግሊፊክ እና የመሶጶታሚያው ኩኒፎርም በመባል የሚታወቁ ናቸው፡፡ በዓለም ውስጥ ያሉት ፊደሎችም በሙሉ ከእነዚህ ሥዕላዊ ምልክቶች የተገኙ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
የግብፅን ሂሮግሊፍክ (ሥዕላዊ ጽሑፍ) መሠረት በማድረግ፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት 1800-1500 በሴማውያን ከተፈለሰፈው ጥንት ሲናዊ (Proto - sinaific) ፊደል፣ በርካታ ሌሎች ፊደላት መገኘት ችለዋል፡፡ ከተፈለሰፉት መካከል ግን እንደ ዐረብኛ፣ ዕብራይስጥኛና ኢትዮጵያዊኛ ያሉት እናት ፊደላቸውን መምሰል እየተውና እየራቁ በመሔድ የተገኙ ናቸው፡፡
የሴም ፊደሎች ሰሜን ሲናዊ እና ደቡብ ሲናዊ በመባል በሁለት  ወገን ይከፈላሉ፡፡ እናም ለኢትዮጵያዊው ፊደል (ግዕዝ) መነሻ ሆኖአል የተባለው የሳባ ፈደል በደቡቡ ሴማዊ ክፍል የሚገኝና በደቡብ ዐረብ የነበረ ነው፡፡
ይህ በደቡብ ዐረብ ይሰራበት የነበረውና ኋላም ወደ ኢትዮጵያ ተሻግሮ የግዕዝን ፊደል ያስገኘው የሳባ ፊደል፣ ሃያ ዘጠኝ ሆሄያት እንደነበሩት ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ግዕዝ ይኸንን የአጻጻፍ ስልት በወረሰበት ጊዜ ሁሉንም አልተቀበላቸውም፡፡ ምክንያቱም በሁለቱ ቋንቋዎች ማለትም በሳባና በግዕዝ ድምፀ ልሳኖች ውስጥ አንዳንድ ድምፆች ልዩነት ስለነበራቸው ነው፡፡
ከዚህም የተነሣ ግዕዝ አምስቱን በመተው፣ ሃያ አራቱን የሳባ ፊደል ሆሄያት ሊወርስ ችሏል፡፡ በተጨማሪም ከንፈራዊ ደወል የለሽ (ፐ) እና አንድ ከንፈራዊ ፈንጂ (ጰ) የተባሉትን ሁለት ድምፀ ወካይ ምልክቶች በማከል የፊደል ሆሄያቱን ቁጥር ኻያ ስድስት አድርሶታል፡፡ እንዲሁም ኻያ ስድስቱ ሆሄያት ድምፅ ሰጪ እንዲኖራቸው በመደረጉ፣ በጠቅላላው (26x7) አንድ መቶ ሰማንያ ሁለት ሆኑ ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የግዕዝ ዲቃላ የሚባሉ ሌሎች አራት ሆሄያትም በመኖራቸውና እነሱም በበኩላቸው አምስት ድምፅ ሰጪዎች ስላሏቸው (4x5) ሃያ ዲቃላ ሆሄያት ስለሚሆኑ፣ የግዕዝ ፊደል በጠቅላላው 202 ሆሄያት ነበሩት፤ አሉትም፡፡
የግዕዝ ፊደል የሚባሉት 26ቱ ድምፆችና አራቱ ዲቃሎች የሚከተሉት ናቸው፡-
ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ፣ ሠ፣ ረ፣ ሰ፣ ቀ፣ በ፣ ተ፣ ኀ፣ ነ፣ አ፣ ከ፣ ወ፣ ዐ፣ ዘ፣ የ፣ ደ፣ ገ፣ ጠ፣ ጰ፣ ጸ፣ ፀ፣ ፈ፣ ፐ እንዲሁም ኰ፣ ጐ፣ ቈ፣ ኈ ናቸው፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት በተለይም 26ቱ የግዕዝ ፊደል ተነባቢ ድምፆች የየራሳቸው የሆነ ትርጉምና የአጠቃቀም ህግ አላቸው፡፡ የጋዜጣውን ዓምድ ላለማጣበብ ሲባል እንጂ ሁሉንም መዘርዘር በተቻለ ነበር፡፡
የግዕዝ ፊደል ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ በር ከፋች ሆኖ በስፋት ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ በኋላ እጅግ በርካታ ድርሳናት ተደርሰውበታል፡፡ በግዕዝ ቋንቋና ፊደል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ቅዱሳት መጻሕፍትዋ ላይ የጻፏቸውን ጨምሮ  የአያሌ መጣጥፎችና መጻሕፍት ደራሲ የሆኑት ምሁር ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ በሐመር መጽሔት ሐምሌ/ነሐሴ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም እትም፤ “… ኢትዮጵያ በጥንታዊው የሥነ ጽሑፍ ታሪክ በዓለም የመጀመሪያውን ረድፍ የምትይዝ አገር ናት፡፡ በእንግሊዝ፤ በፈረንሳይ፣ በጀርመን ዛሬ የሚፃፉት ሁሉ ከኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ በኋላ የመጡ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ጋር የሚወዳደሩት ትልልቆቹ የግሪክ፣ የአራማይክ፣ የላቲን፣ የመሳሰሉቱ ናቸው፡፡ …” በማለት ኢትዮጵያን ታላቅ ከሚያደርጓት ሀብቶቿ አንዱ ይኸው የግዕዝ ሥነ ፅሑፍ መሆኑን በዝርዝር መግለፃቸውን እናያለን፡፡
በጥቅሉ ስለ ግዕዝ ፊደል የትመጣነትና አገልግሎት በዝርዝር ለማስቀመጥ ሰፊ ቦታና ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ለመግቢያ ያህል ይህችን ታህል ካልን የሚበቃ ይመስለኛል፡፡ እናም ዘመቻ ወደበዛበት ወደ አማርኛ ፊደል መለስ ብለን ማየት እንሞክር፡፡
የአማርኛ ፊደል ለአማርኛ ቋንቋ መጻፊያነት እንዲያገለግል ሆኖ ሥራ ላይ መዋል የጀመረው በ1270 ዓ.ም የዛጌ ሥርወ መንግስት ማብቂያ ዘመን አካባቢ መኾኑ ይነገራል፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ፊደሉን የወረሰው በቀጥታ በግዕዙ ከሚገኙት ሆሄያት ነው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን ሃያ ስድስቱንም የግዕዝ ሆሄያት አንድም ሳያስቀር ሁሉንም ተቀብሏቸዋል፡፡
ያደረገው አዲስ ነገር ቢኖር ለቋንቋው የሚያገለግሉ 7 ድምፃዊ ምልክቶችን (የድምፅ ወካዮችን) ጨምሮ የፊደሉን ቁጥር ወደ 33 ከፍ አድርጎ መጠቀም መቻሉ ነው፡፡
እነዚህም ተጨማሪ ያደረጋቸው ሆሄያት “ሸ”ን ከሰ፣ “ቸ”ን ከተ፣ “ኸ”ን ከከ፣ “ኘ”ን ከነ፣ “ዠ”ን ከዘ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ በመጨረሻም ከ“በ” ሆሄ “ቨ” የሚለውን ወካይ ጨምሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ ስንመለከተው፣ አማርኛ የራሱ የሆነ ፈደል አለውን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይከብዳል ተብሎ አይገመትም፡፡ አንድ ቋንቋ ወይም አገር የራሱ ፊደል አለው ብሎ መናገር የሚቻለው የቋንቋውን ድምፆች የሚወክሉ ሆሄያትን  የያዘ ፊደል መፈልሰፍ ሲችል ነው፡፡ ስለሆነም አማርኛ የሚጠቀምበት ፊደል 78.8% የግዕዝ በመሆኑ ፊደሉ የአማርኛ ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ከዚህም የተነሣ አማርኛ በግዕዝ ፊደል ላይ በጨመራቸው 7 ሆሄያት ብቻ የቋንቋውን ድምፆች በጽሑፍ መግለጽ ስለማይችል የራሱን ፊደል ይዟል አይባልም፡፡
ከዚህም ላይ አማርኛ ከግዕዝ የወረሰው ፊደሉን ብቻ አይደለም፡፡ ከቋንቋውም ቀላል የማይባሉ ቃላትን በመዋስ ሲጠቀምባቸው ቆይቷል፤ እየተጠቀመባቸውም ነው፡፡ ይህ ከሆነ ታድያ “የአማርኛ ፊደል ይሻሻል፤ ፊደላት በዝተዋልና ይቀነሱ” ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችና ዘመቻዎች ለምን ይነሳሉ? በቀጣይ የምንመለስበት ይሆናል፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡  

Published in ጥበብ

     በ21 ኢትዮጵያዊያን የተመሰረተውና ነዳጅ በማከፋፈል የመጀመሪያው አገር በቀል ድርጅት የሆነው የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም አክሲዮን ማህበር ለዋና መስሪያቤትነት ባለ 11 ፎቅ ህንፃ ሊገነባ ነው፡፡ ድርጅቱ ከትናንትና በስቲያ ሲኤምሲ በሚገኘው ማደያ ግቢ ውስጥ የተመሠረተበትን 10ኛ ዓመት በዓል ከባለ አክሲዮኖቹ ጋር በድምቀት ያከበረ ሲሆን የመስኖ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ የህንፃውን የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡ 50 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተገመተው ህንፃ፤ ከዋና መስሪያ ቤትነት በተጨማሪ ለተለያዩ አገልግሎቶችም ይውላል ተብሏል፡፡ 261 ባለአክሲዮኖችና የተከፈለ 135 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያለው የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም፤ በመላ አገሪቱ መቶ ያህል ማደያዎች ያሉት ሲሆን ከአንድ ሺህ በላይ ለሆኑ ቋሚና ጊዚያዊ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠሩን የድርጅቱ ዋና የስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መኮንን በእለቱ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጥራት ያለው ነዳጅ ከማከፋፈሉም በላይ ጥራት ያላቸው የብሪቲሽ ፔትሮሊየምን የሞተር ዘይቶች በብቃት እንደሚያከፋፍል የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ የነዳጅ ማደያ ምልክቱንም ቢሆን በአንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ አሰርተው ማስገጠማቸውን ተናግረዋል፡፡ የውሃ የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ባደረጉት ንግግር፤ አገር በቀል ድርጅቶች ነዳጅ ቢያከፋፍሉ ለአገር ጠቀሜታ ያለውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት በጥቅምት ወር 1996 ዓ.ም በሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ብሔራዊ ፔትሮሊየም ወደ ዘርፉ በመግባት ከፍተኛ እድገት እንዳመጣ ገልፀው ለመስራቾቹ፣ ለባለአክሲዮኖችና ለድርጅቱ ሰራተኞች ለዚህ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡ ድርጅቱ የ10ኛ ዓመት ምስረታውን አስመልክቶ ባዘጋጀው በዓል የተለያዩ አስተዋፅኦዎች ላበረከቱ ወገኖችና ሠራተኞች ሽልማት አበርክቷል፡፡ ለዋና መስሪያ ቤትነት የሚገነባው ህንፃም በሁለት ዓመት ተጠናቅቆ ስራ እንደሚጀምር ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

“ቢራ ሃንግኦቨር የሚፈጥረው ፈርሜንቴሽኑን ካልጨረሰ ነው”

    ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ከየሚዲያው የተውጣጡ ጋዜጠኞች፣ የአዲስ አበባ የጤና ቡድን አመራሮችና ሌሎች እንግዶች ቢጂአይ ኢትዮጵያ ባደረገላቸው ግብዣ መሰረት፣ የዝዋይን የወይን ጠጅ እርሻና ፋብሪካ እንዲሁም የሀዋሳን የቢራ ፋብሪካ ጎብኝተው ነበር፡፡ እኔም ከጐብኚዎቹ አንዱ ነበርኩ፡፡በመጀመሪያ የጎበኘነው ዝዋይ የወይን እርሻና ፋብሪካ ነው፡፡ ወይን የሚመረተው በዓመት አንዴ ስለሆነ ጠመቃውም አንድ ጊዜ ነው፡፡ የዕለት ተዕለት የሥራ ሂደት ያለው ቢራው ስለሆነ በዚያ ላይ አተኩራለሁ፡፡ እናንተ! ይኼ በየመጠጥ ቤቱ የምንጠጣው ድራፍትና ቢራ በርካታ ሂደቶች አልፎ ነው ለካ የሚቀርብልን፡፡ ውሃው በተለያዩ ኬሚካላዊ ሂደት ውስጥ አልፎና ተጣርቶ፣ መጥመቂያ ጋኖቹም በኬሚካሎች ታጥበው፣ ንፁህ መሆናቸው በላብራቶሪ ፍተሻ ተረጋግጦ ነው ቢራ ጠመቃው የሚጀመረው፡፡
ለቢራ ምርት የሚያስፈልጉት አራት ነገሮች ውሃ፣ የቢራ ገብስ (ብቅል) ጌሾና እርሾ ናቸው፡፡ የትኛውም የቢራ ፋብሪካ የሚያስፈልጉት ዋነኛ ንጥረ ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡ ልዩነት የሚፈጠረው በአቀማመም ሂደት ነው፡፡ የቢራ ጠመቃ የሚጀመረው ገብሱን (ብቅሉን) በመፍጨት ነው፡፡
 የሃዋሳው ቢጂአይ ቢራ ፋብሪካ ለአንድ ጊዜ ጠመቃ 5,950 ኪሎ የገብስ ብቅል እንደሚፈጭ የፋብሪካው የፕሮዳክሽን ቺፍ ሊደር አቶ ደገፋው ማዘንጊያ ገልፀዋል፡፡ ወፍጮው አውቶማቲክ ስለሆነ ገብሱን ራሱ በማበጠር ጠጣር ነገሮችን (አፈር፣ ብረት…) እንዲሁም ገለባ ይለያል፡፡ ከዚያም ዱቄቱ በ13.500 ሊትር ይቦካና በተለያዩ የሙቀት ደረጃዎች እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ የቢራ ጥራት የሚወሰነው፤ በገብሱ ሽርክትና መጠን እንደሆነ አቶ ደገፋው ይናገራሉ፡፡ ፋብሪካው 12 ጋኖች ሲኖሩት እያንዳንዱ ታንክ 200ሺ ሊትር ሃይ ግራቪቲ ቢራ እንደሚይዝ፣ ፈርሜንቴሽን (ማብላያ) ጋን ውስጥ ከ15-20 ቀን እየተብላላ እንደሚቆይ፣ በመጀመሪያው ፈርሜንቴሽን ለ7 ቀናት በ12 ዲግሪ ሙቀት፣ በሁለተኛው በ16 ዲግሪ ሙቀት ለ72 ሰዓታት እንደሚቆይና ከሦስት ቀናት በኋላ ተጣርቶ ለገበያ እንደሚቀርብ ሃላፊው አስረድተዋል፡፡
የድራፍትና ቢራ የአመራረት ሂደት አንድ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ልዩነት የሚመጣው በፓስቸራይዜሽን ሲስተሙ፣ በመያዣ ዕቃ (ፓኬጂንግ) በርሜልና ጠርሙስ መሆንና በካርቦንዳይ ኦክሳይድ ይዘት እንደሆነ ገልጿል፡፡ ድራፍት የሚቀቀለው (ፓስቸራይዝ የሚደረገው) በ94 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲሆን ቢራ ደግሞ በ62 ዲግሪ ረዘም ላለ ጊዜ ነው፡፡ ድራፍትም ሆነ ቢራ የሚቀቀሉት (ፓስቸራይዝድ የሚደረጉት) ሳይበላሹ የመቆያ ጊዜያቸውን ለማራዘም እንደሆነ የጠቀሱት ሺፍ ኃላፊው፤ ፓስቸራይዝድ የተደረገ ቢራ ሳይበላሽ ለአንድ ዓመት፣ ድራፍት ደግሞ ለአንድ ወር ይቆያሉ ብለዋል፡፡
የቢራ ሃንግኦቨር (በማግስቱ ራስ ምታት) የሚፈጠረው በፈርሜንቴሽን ጊዜ ቆይታ ማነስ ወይም መብዛት እንደሆነና ጊዜውን በመቆጣጠር ማስቀረት እንደሚቻል አቶ ደገፋው አስረድተዋል፡፡ ለምሳሌ ቢራው ውስጥ ብዙ ጉሉኮስ (ስኳር) እያለ የፈርሜንቴሽኑ ጊዜ አጭር ከሆነ (በደንብ ካልተብላላ) ከፍተኛ አልኮሎች ይመረቱና ቢራው ሲጠጣ ራስ ምታት ያመጣል፡፡ ፈርሜንቴሽን በጣም እንዲዘገይም ሆነ እንዲፈጥን አይደረግም፡፡ ከገበያ አኳያ እንዲዘገይ፣ ከጥራት አኳያ እንዲፈጥን ማድረግ ጥሩ አይደለም፡፡ ሲዘገይም ሆነ ሲፈጥን የሚፈጠር ነገር (ያልተፈለገ ምርት) አለ፡፡ ያ ነው ራስ ምታት የሚፈጥረው በማለት አስረድተዋል፡፡
ሴላር የሚባለው ፈርሜንቴሽኑን ያልጨረሰና የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ ያልያዘ በጣም ወፍራም ቢራ ነው ይላሉ - አቶ ደገፋው፡፡ የአልኮል መጠኑ ከፍተኛ፣ እንዲሁም በጣም ወፍራምና ያልተጣራ ስለሆነ ገበያ ላይ ቢወጣ ብዙ ሰው አይጠጣውም፡፡ ስለዚህ አልኮሉ እንዲቀንስ (ዳሊዩት) ይደረጋል፤ ይጣራና ተገቢውን የውፍረት መጠን ይዞ ወደ ገበያ ይወጣል ብለዋል፡፡
ሴላር መጠጣት ወይም አለመጠጣት የደንበኛው ፍላጎት ነው፡፡ ነገር ግን ሴላር ገበያ ሲወጣ ከቢራ እኩል አይሸጥም፤ ዋጋው ወደድ ይላል፡፡ ፓስቸራይዝድ ስላልሆነ ለጤናማም ጥሩ አይደለም፡፡ ሴላር ወዲያው ካልተጠጣና ሁለት ሦስት ቀን ከቆየ ይበላሻል፡፡ ስለዚህ ሴላር መጠጣት ካለበት ፋብሪካው አካባቢ፣ የሚጓጓዝበትም መኪና ማቀዝቀዣ ያለው መሆን አለበት በማለት አቶ ደገፋው ማዘንጊያ አብራርተዋል፡፡  


Page 3 of 13