“የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰራተኞች አሉባልታ ነው” - ዩኒቨርስቲው

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ አስተዳደራዊ ችግር መማረራቸውን የተናገሩት የዩኒቨርስቲው ሠራተኞች፤በየጊዜው  መምህራን ሥራቸውን እየለቀቁ እንደሚወጡ ገለፁ፡፡ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ በበኩላቸው፤ የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰራተኞች አሉባልታ እንጂ በዩኒቨርስቲው ውስጥ አስተዳደራዊ ችግር እንደሌለ  ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በዓመት ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የሚመደብለት፣ ከ45 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሚያስተምርና ከአምስት ሺህ በላይ ሰራተኞች የሚያስተዳድረው ዩኒቨርስቲው፤ ከአመራርና አስተዳደር ሙያ ጋር የተገናኘ የትምህርት ዝግጅት በሌላቸው አመራሮች እየተመራ፣ ለከፍተኛ አስተዳደራዊ ችግር መጋለጡን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡
 አንድ የዩኒቨርስቲው ሠራተኛ በሰጠው አስተያየት፤ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ በፊዚክስ፣ምክትሉ ዶ/ር ፍሬው አሞኜ በእንስሳት ህክምና፣ሌላው ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር እያዩ  በባዮሎጂ የተመረቁ መሆናቸውን በመጠቆም፣ አንዳቸውም በአስተዳደር ወይም በአመራር ሙያ አለመመረቃቸውን አስረድቷል፡፡ “አመራሩ ለምን በተፈጥሮ ሳይንስ ምሁራን በሞኖፖል እንደተያዘ አልገባኝም” ብሏል፡፡ የፕሬዚዳንትና የምክትል ፕሬዚዳንቶቹ እርስ በእርስ አለመግባባትና በየስብሰባው መዘላለፍ ሌላው የአስተዳደሩን ችግር ያባባሰ ጉዳይ መሆኑን የሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ የአመራሮቹ ውዝግብ በተቀረው ሰራተኛ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አልሸሸጉም፡፡
ዩኒቨርስቲው ከ159 ሚሊዮን ብር በላይ አውጥቶ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ለመምህራን ኮንዶሚኒየም ቤቶች ቢገዛም እስካሁን  ለመምህራኑ አላስረከበም ሲሉ የሚወቅሱት ሠራተኞቹ ፤ህንፃዎቹ ያለ አገልግሎት ቆመው እየተሰነጣጠቁና ለመፀዳጃነት እየዋሉ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ዩኒቨርስቲው እስካሁን ወደ 20 ሚሊዮን ብር መክሰሩንና ህንፃዎቹን ለማደስ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠብቀው ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው አመራር፣ የመምህራርንንም ሆነ የሌሎች ሠራተኞችን ቅሬታ ለመስማትና መፍትሄ ለማበጀት ዝግጁ አይደለም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በዚህም የተነሳ በተለይ ወጣቶችና ትዳር ያልያዙ መምህራን በአስተዳደራዊ ችግር እየተማረሩ በየጊዜው ሥራቸውን እየለቀቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው ሁለት ምክትል ዲኖችም ከመማረራቸው የተነሳ የአገልግሎት ክፍያ ሳያገኙ ሥራቸውን ጥለው እንደወጡ ገልፀዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ በበኩላቸው፤ ሠራተኞች የሚለቁት የተሻለ ደሞዝ ሲያገኙ እንጂ በአስተዳደራዊ ችግር እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ አስተዳደራዊ ችግር እንዳለ የሚያወሩት የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰራተኞች እንደሆኑም ገልፀዋል - ፕሬዚዳንቱ፡፡ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ በአገር ውስጥ ካሉት ምርጥ ዩኒቨርስቲዎች ከሦስተኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ዶ/ር ባይሌ፤  የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በቀጥታ ከዩኒቨርስቲው በርካታ ምሩቃንን እንደሚቀጥሩ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው አመራር የትምህርት ዝግጅት፣ ከአስተዳደር ሙያ  ጋር ስለማይገናኝ ዘርፈ ብዙ አስተዳደራዊ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው በሚል የተነሱ ቅሬታዎችንም ፕሬዚዳንቱ አይቀበሉትም። “ማንኛውም ሰው የመጀመርያ ድግሪውን በየትኛውም ዘርፍ ሊሰራ ይችላል፤ ለምሳሌ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር የመጀመርያ ድግሪ ከአመራር ጋር የተገናኘ አይደለም” ያሉት ዶ/ር ባይሌ፤ አንድ ሰው ተመራማሪ መሆኑ ከአመራርነት አያግደውም ሲሉ ተሟግተዋል፡፡ እኔ የፊዚክስ ሰው ስለሆንኩ መምራት አልችልም ማለት አይደለም ያሉት ዶ/ሩ፤ ይሄ የሚያሳየው የቅሬታ አቅራቢዎቹን አላዋቂነት ብቻ ነው ብለዋል፡፡ የፕሬዚዳንቶቹን አለመግባባትና መዘላለፍ በተመለከተ ሲያስረዱም ፤ በሃሳብ አለመግባባትና የሃሳብ ልዩነትን እንደተራ ጠብ ማየት የግንዛቤ ችግር ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ዋናው ለአላማ መሥራት እንጂ የሰዎች ግንኙነት መሆን የለበትም  ብለዋል፡፡    
ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ለመምህራን የተገዙትን ቤቶች በተመለከተ ሲመልሱም “ዩኒቨርስቲው ቤት ለመግዛት ብር ከፈለ እንጂ ቤት አይገነባም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ መረጃ ሰጪዎቹ ያለ እውቀት ወሬ ይዘው የሚሮጡ በመሆናቸው ነው እንጂ ችግሩ የተከሰተው በቤቶች ልማት አቅም ማነስ እንደሆነ ተረጋግጦ፣ ዩኒቨርስቲው የቤቶቹን የማጠናቀቂያ  ሥራ ለመሥራት ውሳኔ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ዩኒቨርስቲው የገዛውን ይሄንኑ ኮንዶሚኒየም ለመምህራኑ ሳያስረክብ በመቅረቱ  ዩኒቨርስቲው ለ20 ሚሊዮን ብር ኪሳራ መዳረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

         የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮና መኖርያ ቤት በሚገኝበት ታላቁ ቤተ መንግሥት አጥር ዙሪያ ገባው ላይ የሚገኘው የመስቀል ቅርጽ፣ የእስልምናና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ሃይማኖቶች መሪዎችን አነጋገረ፡፡
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ በሐዋሳ ባካሔደው የምክክር መድረክ ላይ ‹‹አገሪቱና መንግሥቱ የእኩልነትና የዜጎች መንግሥት ነው፤›› ያሉት የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ኪያር ሙሐመድ አማን÷ ከቀድሞው ሥርዐት አንጻር አሁን የሚያበረታቱ ነገሮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
ይኹንና በሴኩላሪዝምም ቢኾን ፍጹምነት ባለመኖሩ ‹‹አገር የጋራ ነው ከተባለ በኋላ የጎደለ ነገር አለ፤›› በሚል አዘውትረው ጥያቄ የሚያቀርቡላቸው ሰዎች መኖራቸውን ሸኽ ኪያር ጠቅሰዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ይቀርቡልኛል ካሏቸው ጥያቄዎች መካከል ‹‹ለምሳሌ፡- ታላቁ ቤተ መንግሥት በመስቀል ነው የተከበበው፤ ይህ መጥፎ ነገር ሊያመለክት ይችላል›› የሚሏቸው እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
ታላቁን ቤተ መንግሥት የከበበውን መስቀል፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ፊት ለፊት እንደቆመው የደርግ ሐውልት ያህል እንዲታይ በሚል ለጥያቄው መልስ እንደሚሰጡ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፣ “በአክሱም አንዲት ጎጆ መስጊድ እንኳ ለመገንባት እንዴት አልቻልንም?” ተብለው ሲጠየቁ የዚህን ያህል ‹‹የቀልድ መልስ እንኳ ለመስጠት አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገሮችን ለማከም መቅደድ አለብን›› የሚል የዐረብኛ ብሂል እንዳለ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ሁልጊዜ ጥላሸት መስለው ይታያሉ ያሏቸውን ችግሮች ለመፍታትና መልስ ለመስጠት ይቻላል ወይስ አይቻልም ሲሉ በፈገግታ የታጀበ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
በጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸኽ ኪያር ጥያቄ ላይ ፈጥነው አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ሸኽ ኤልያስ ያቀረቧቸው ነገሮች ሌሎች ስለጠየቋቸው እንጂ ራሳቸው ፕሬዝዳንቱ አምነውበት እንዳልሆነ ከአነጋገራቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጥያቄው ስለ መስቀልም ስለ አክሱምም መነሣቱን ያስታወሱት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ሁለቱም የቆዩ ናቸው እንጂ አሁን የተፈጠሩ አይደሉም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፤ ‹‹በዚህ ግቢ (ስብሰባው በተካሔደበት ሌዊ ሪዞርት ማለታቸው ነው) ያየናቸው ዋርካዎች ድሮ የነበሩ ናቸው፤ አሁንም ይጠቅማሉ፤ ከቆረጥናቸው ጉዳት ነው፤ ከኖሩ ይጠቅሙናል፤›› በማለት የቆየው ታሪክ መጠበቅ እንዳለበት በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የመስቀሉ ቅርጽ የቆየ ታሪክ ነው፤ በታሪካዊነቱ ተከብሮ ተጠብቆ መኖር አለበት፤ በአክሱም ስላለው ነገር ከተነሣም የእኛም ጥያቄ ወደ ረጅምና ዝርዝር ነገር ይሔዳል፤›› በማለት የሁሉም ታሪክ በየራሱ መታወቅና መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
መከባበርም መቻቻልም እጅግ አስፈላጊ  መሆኑን የገለፁት ፓትርያርኩ፣ “አገሩ የኹላችንም ነው፤ የነበረው ታሪክ ደግሞ በታሪካዊነቱ ተከብሮ መኖር አለበት” በሚል ለሸኸ ኪያር ጠያቂዎቹ ምላሽ መስጠት እንደሚቻል በፈገግታ የታጀበ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የውይይቱ ተሳታፊ ከኾኑ ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችም ሆነ የምክክር መድረኩን ከመሩት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች የተሰጠ ምላሽና አስተያየት አልነበረም፡፡
የመስቀልና ዘውድ አምሳል በተቀረጹባቸው አጥሮች የተከበበው ታላቁ ቤተ መንግሥት፣ የምኒልክ ቤተ መንግሥት በመባል የሚታወቅ ሲሆን ንጉሡ በ1878 ዓ.ም ያሠሩት መንበረ መንግሥታቸው ነበር፡፡ የተለያዩ መኖርያ ቤቶችን፣ እልፍኞችንና አዳራሾችን እንዲሁም ቤተ ጸሎቶችን ያካተተው ቤተ መንግሥቱ÷ የታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም፣ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እና የሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ይዋሰኑታል፡፡
በተለይ የዘውድ አምሳል በጉልላቱ ላይ የሚታይባት የበኣታ ለማርያም ገዳም የንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፣ የንግሥታቱ እቴጌ ጣዪቱና ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንዲሁም የልዕልት ፀሐይ ኃይለ ሥላሴ ዐፅሞች ያረፉበት ሲኾን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮና መኖርያ የኾነው ከደርግ መንግሥት ጀምሮ ነው፡፡
ለሁለቱ የሃይማኖት መሪዎች መነጋገርያ የኾነው ጉዳይ መነሻ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ የግጭትና ሰላም ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር በኾኑት ዶክተር ታረቀኝ አዴቦ የቀረበው ‹‹በአገራችን የሃይማኖት ተቋማትና ተከታዮች በሰላም አብሮ የመኖር ወርቃማ ተሞክሮና የማስቀጠል ፋይዳው›› የተሰኘ ፅሁፍ ነው፡፡
የአገራችን ሕዝቦች ‹‹እንኳን በብርሃን ዘመን በጨለማው ዘመንም ጭምር›› የሃይማኖት ብዝሐነትን በመሠረቱ ያለመግባባትና የግጭት መነሻ ሳያደርጉ በሰላም አብረው እንደኖሩ የሚያትተው የጥናት ጽሑፉ፣ በሰላም አብሮ መኖር÷ ብዝሐነትን እንደ ነባራዊ ኹኔታ የመቀበል፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል ስልት የመከተል፣ የብዝሐነቶች ነጻነትና እኩልነት መረጋገጥ አስተሳሰቦች ጥምረት መኾኑን ይገልጻል፡፡
የሃይማኖት መሪዎች በሰላም አብሮ የመኖር አርኣያ በመኾን ከቅድመ አያቶቻችን ጀምሮ ለዘመናት የቆየውን በሰላም አብሮ የመኖር ዕሴት በውስጣቸውም ይኹን በመካከላቸው፣ አስተሳሰቡንና ተግባሩን በማስፈን ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ ታሪካዊ አደራና የዜግነት ግዴታ እንዳለባቸው ያስገነዝባል- ጥናታዊ ፅሁፉ፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት፣ ያለፈውን ታሪካዊ እውነታ ተቀብሎና ዕውቅና ሰጥቶ፣ የወቅቱን ነባራዊ ኹኔታ መሠረት አድርጎ ወደፊት በመቃኘት፣ በአገራችን ብዝሐነትን ተቀብሎ በተገቢው ኹኔታ ለማስተናገድ አቅጣጫ ያስቀመጠ ብቸኛው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ነው የሚሉት ሌሎች የጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎች÷ መንግሥታዊ ሃይማኖትን ከሠየመው የንጉሣዊው ሥርዐት ሕገ መንግሥትና ፀረ - ኹሉ ከነበረው የወታደራዊ ሥርዐት ሕገ መንግሥት፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት የሚለይባቸውን መርሖዎችና ድንጋጌዎች ዘርዝረዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ለተከታዮቻቸው የማስተማር ሓላፊነታቸውን በተጠናከረ መልኩ መወጣት ይኖርባቸዋል ያሉት ጽሑፍ አቅራቢዎቹ፣ የመንግሥትና የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትና ሠራተኞችም ሴኩላሪዝምንና ሃይማኖት ነክ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በጥብቅ በመተግበር፣መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን ያረጋገጠውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ማስከበር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

Published in ዜና

            በቀድሞው የሃገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊ አቶ ወልደሥላሴ ወ/ሚካኤልና የቅርብ ዘመዶቻቸው ላይ የቀረበውን የሙስና ክስ፣አቃቤ ህግ እንደገና አሻሽሎ ያቀረበ ሲሆን የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው፤ ማሻሻያው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት የቀረበ አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
ቀደም ሲል አቃቤ ህግ፣ በደህንነት ኃላፊውና በክሱ በተካተቱት ወንድምና እህታቸው እንዲሁም የቅርብ ወዳጃቸው ላይ ባቀረበው ክስ፣ የአቶ ወ/ሥላሴ ሃብት ወደ ሌሎች ተከሳሾች ተላለፈ የተባለበት መንገድ ግልፅ አይደለም በሚል ጉዳዩ ተብራርቶ እንዲቀርብ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ባለፈው ሰኞ  አቃቤ ህግ ማሻሻያውን ለጽ/ቤቱ በፅሁፍ አቅርቧል፡፡
ማሻሻያውን የተመለከቱት የተከሳሽ ጠበቆችም፣ ማሻሻያው በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት የቀረበ አይደለም፣ ግልፅ ባለመሆኑ ለመከላከል ያስቸግራል የሚል ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ ፍ/ቤቱም የጠበቆቹን ቅሬታ ከተቀበለ በኋላ  አጣርቶ ትዕዛዝ ለመስጠት ለየካቲት 13 ቀን 2006 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በቀድሞው የደህንነት መስሪያቤት ኃላፊ አቶ ወ/ሥላሴና የመከላከያ ሰራዊት ባልደረባ በነበረው ወንድማቸው አቶ ዘርአይ ወ/ሚካኤል እንዲሁም በእህታቸው ወ/ት ትርሐስ ወ/ሚካኤልና በቅርብ ጓደኛቸው አቶ ዳሪ ከበደ ስም የመኖሪያ ቦታን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶችንና በአጠቃላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ይዞ መገኘት በሚል መከሰሳቸው ይታወሳል፡፡    



Published in ዜና

“በሁሉም ማዕከላት አገልግሎቱ ያለእንከን እየተሰጠ ነው”

በአዲስ አበባ ተግባራዊ በተደረገው የቅድመ ክፍያ የመብራት አገልግሎት አሰጣጥ ደንበኞች መማረራቸውን እየገለፁ ሲሆን መብራት ሃይል በበኩሉ፤ በሁሉም ማዕከላት አገልግሎቱ ያለእንከን እየተሰጠ ነው ብሏል፡፡
ካዛንቺስ በሚገኘው የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ማዕከል፣በክፍያ አሰባሰብ ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ ያገኘናቸው አንዳንድ ተገልጋዮች፤ ክፍያው የሚሰበሰበው በአንድ ሠራተኛ ብቻ በመሆኑ ወረፋ በመጠበቅ የስራ ጊዜያቸውን እያባከኑ እንደሆነ በምሬት ገልፀዋል፡፡ ረጅም ወረፋ ሲጠብቁ ቆይተው  የምሣ ሰአት አሊያም የስራ መውጫ ደርሷል እየተባሉ ወደ ቤታቸው የሚመለሱ በርካታ ደንበኞች እንዳሉ የታዘበ አንድ ወጣት የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ደንበኛ፤ እሱም ራሱ በተመሳሳይ ምክንያት ለሶስት ተከታታይ ቀናት ወደ ማዕከሉ መመላለሱን ገልጿል።
ከሃያት አካባቢ የአገልግሎት ካርዳቸውን ለማስሞላት ካዛንቺስ ድረስ መምጣታቸውን የገለፁት አንድ ጎልማሳ በበኩላቸው፤ ድርጀቱ በከተማዋ አንድ ማዕከል ብቻ በመክፈቱ እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ተገልጋዮች ለእንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል። የአገልግሎቱ መጀመር በተለይ የመብራት አጠቃቀምን በዘመናዊ መልኩ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የሚገልፁት ደንበኞች፤ መብራት ሃይል በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ማዕከላትን በስፋት በመክፈት፣ አገልግሎቱን በተደራጀ የሰው ሃይል በመስጠት ደንበኞችን ከእንግልትና ከምሬት መገላገል ይችላል  ብለዋል፡፡
የደንበኞችን ቅሬታና በአጠቃላይ አገልግሎቱን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽን የውጭና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ፤አገልግሎቱ ከሁለት አመት በፊት እንደተጀመረና የደንበኞችን ወጪና ጊዜ ለመቆጠብ ታስቦ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው፤ በከተማዋ አገልግሎቱን የሚሰጡ 29 ማዕከላት እንዳሉ፣ ሁሉም አገልግሎቱን በተቀላጠፈ መልኩ ለ174ሺ35 ደንበኞች ያህል እየሰጡ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዳማ ያሉት 3 ማዕከላት እና በቢሾፍቱ ያሉት 2 ማዕከላት፣ በአጠቃላይ ለ26ሺ39 ደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡ የቢል ህትመት ወጪን እንዲሁም የቆጣሪ አንባቢንና የገንዘብ ሰብሳቢን ድካም በማስቀረት ረገድ አዎንታዊ ሚና እንዳለው የሚነገርለት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ አገልግሎት ተግባራዊ በተደረጉባቸው ሶስቱ ከተሞች ለ200ሺ104 ደንበኞች አገልግሎት እየተሰጠ እንደሆነም አክለው  ገልፀዋል፡፡
በከተማዋ አንድ የአገልግሎት ማዕከል ብቻ በመኖሩ ተቸግረናል የሚለውን የደንበኞች ቅሬታ አስመልክቶ  የተጠየቁት አቶ ምስክር ሲመልሱ “ካዛንቺስና ሜክሲኮ ያሉት እንደ ዋና ማዕከል እሁድን ጨምሮ አገልግሎት የሚሰጥባቸው እንጂ ብቸኛ ማዕከላት አይደሉም፤ በከተማዋ ያሉት 29 ማዕከላት በቂ ሙያተኛ ተመድቦላቸው አገልግሎቱን በተቀላጠፈ መልኩ እየሰጡ ነው” ብለዋል፡፡ በቅርቡም የሃይል ብክነትን  ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሌሎች ዘመናዊ ቆጣሪዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መስሪያ ቤቱ እቅድ መያዙን አቶ ምስክር ጠቁመዋል፡፡  

Published in ዜና

ጊዜው ቢከፋም ለጋሾች እጃቸው አልታጠፈም
50 በጎ አድራጊዎች 7.7 ቢሊዮን ዶላር ለግሰዋል
ከሴቶች ለጋሾች ይልቅ ወንድ ለጋሾች በርክተዋል

በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2013 ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ገንዘባቸውን ከለገሱ አሜሪካውያን መካከል፣ የፌስቡክ መስራቹ  ማርክ ዙከርበርግና ባለቤቱ ፒሪሲላ ቻን ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ክሮኒክል ኦፍ ፌላንትሮፒ የተባለው ተቋም ይፋ አደረገ፡፡
ጥንዶቹ የአመቱን የወደር የለሽ የቸርነት ክብር የተጎናጸፉት፣ ሲሊከን ቫሊ ፋውንዴሽን ለተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት 990 ሚሊዮን  ዶላር ዋጋ ያለው የፌስቡክ የአክሲዮን ድርሻ በመለገሳቸው ነው፡፡ ይህ በአመቱ በአሜሪካ ምድር የተሰጠ ከፍተኛ ልግስና፣ ፋውንዴሽኑን ከአገሪቱ ታላላቅ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተርታ ያሰልፈዋል ተብሏል፡፡
ዙከርበርግና ሚስቱ በአመቱ የአገሪቱ 50 አባ መስጠቶች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት አሜሪካውያን በእድሜ ለጋዎቹ ሲሆኑ በሰላሳ አመት እድሜ ላይ የሚገኙት ጥንዶቹ፣ ባለፉት ሁለት አመታትም ለዚሁ የበጎ አድራጎት ድርጅት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የአክሲዮን ድርሻ በልግስና አበርክተዋል።
ጥንዶቹ የለገሱት ገንዘብ በትምህርትና በጤና ዘርፎች ለሚከናወኑ ስራዎች ይውላል ተብሏል፡፡
ክሮኒክል ኦፍ ፌላንትሮፒ የአመቱ ለጋስ ብሎ በሁለተኛነት ያስቀመጣቸው፣ ቴክሳስ ኢነርጂ የተባለው ኩባንያ የቀድሞ ስራ አስኪያጅ ጆርጅ ሚሼል ናቸው፡፡ ባለፈው ሃምሌ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት እኒህ ባለጠጋ፣ቤተሰባቸው ለበጎ አድራጎት ድርጅት እንዲሰጥላቸው አደራ ብለው በሄዱት 750 ሚሊዮን  ዶላር ነው ለዚህ ክብር የበቁት፡፡
ከናይኪ ኩባንያ መስራቾች አንዱ የሆኑት ፊል ናይት እና ባለቤታቸው ፔኔሎፔም፣ ለኦሪገን ሄልዝ ኤንድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ፋውንዴሽን የካንሰር ምርምር እንዲውል መዥረጥ አድርገው በሰጡት 500 ሚሊዮን  ዶላር ከአገሪቱ የአመቱ ቀዳሚ ለጋሶች ሶስተኛ ሆነዋል፡፡ የአሜሪካን የወደር የለሽ ቸሮች ዝርዝር በቀዳሚነት ሲመሩ የቆዩት የማይክሮ ሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስና ባለቤታቸው ሚሊንዳ ጌትስ፣ በ2013 ክብራቸውን ማስጠበቅ ባይችሉም በአመቱ ከ181 ሚሊዮን  ዶላር በላይ ለግሰዋል ተብሏል፡፡ ጥንዶቹ በ2004 ለበጎ አድራጎት ተግባር ለመስጠት ቃል የገቡትን 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን  ዶላር ቀስበቀስ መክፈል መቀጠላቸው ተነግሯል፡፡
በክሮኒክል ኦፍ ፌላንትሮፒ የ2013 ወደር የለሽ ለጋሶች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት 50 አሜሪካውያን፣ ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች በድምሩ 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ሰጥተዋል - በ2014፡፡
በአመቱ 296 ሚሊዬን ዶላር በመስጠት በለጋሾች ዝርዝር ውስጥ የአምስተኛነትን ደረጃ የያዙት ጆን አርኖልድ እና ባለቤቱ ላውራ፣ ድጋፍ የሚሹ ወገኖቻቸውን ብቻም ሳይሆን መንግስታቸውንም በመርዳት የሚታወቁ ጥንዶች ናቸው፡፡ ባልና ሚስቱ ባለፈው ጥቅምት ወር የአሜሪካ መንግስት መዘጋቱን ተከትሎ በተከሰተ የአቅም ማጣት ችግር ላይ ፈጥነው ደርሰዋል፡፡ መንግስት በወቅቱ ትምህርት ቤቶቻቸው ተዘግተው ቤት ሊውሉ የነበሩ 7ሺህ ያህል አሜሪካውያን ህጻናትን ትምህርት ማስቀጠል የቻለው፣ እነዚህ ጥንዶች ባበደሩት 10 ሚሊዮን  ዶላር ነው፡፡
በአመቱ የለጋሾች ዝርዝር ውስጥ ዙከርበርግን ጨምሮ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሰማሩ ሌሎች አምስት ታዋቂ ግለሰቦችም ተካተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢቤይ መስራች ፔሪ ኦሚድያር፣ የጎግል መስራች ሰርጌይ ብሪንና ከማይክሮሶፍት መስራቾች አንዱ የሆኑት ፖል አለንና ሚስቶቻቸው ይጠቀሳሉ።
ወንዶች በሚበዙበት በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ለጋሾች፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተንገራገጨ ባለበት ወቅት ሳይሰስቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለበጎ አድራጎት ስራ መለገሳቸው ያስደንቃቸዋል ተብሏል፡፡
ለጋሾቹ በአመቱ ከሰጡት ገንዘብ አንድ ሚሊዮን ዶላር ያህሉን የወሰዱት የእርዳታ ድርጅቶች፣ ሆስፒታሎችና ኮሌጆች ሲሆኑ፤ የተቀረውም በህክምና ምርምር፣ ሰብአዊ አገልግሎቶች፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በህጻናትና ወጣቶች ወዘተ ዙሪያ ለሚሰሩ ድርጅቶችና ተቋማት እንደሚውል ተነግሯል፡፡


Published in ዜና

በህፃናት ላይ እየተከሰተ ለሞት የሚዳርጋቸውን የተቅማጥ በሽታ ለማከም የሚረዳና የZinc ንጥረ ነገርን የያዘው ህይወት አድን ጨው ወይም ኦ.አር.ኤስ እጅግ የጐላ ጠቀሜታ እንዳለውና በተቅማጥ ሣቢያ የሚሞቱ ህፃናትን ቁጥር ከግማሽ በላይ ለመቀነስ እንደሚያስችል ተገለፀ፡፡
DKT ኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ በሐርመኒ ሆቴል ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ላይ እንደተገለፀው ለምለም ፕላስ በሚል ስያሜ እየተዘጋጀ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረውና የዚንክ ንጥረ ነገርን የያዘው ህይወት አድን መድሃኒት በተቅማጥ ምክንያት ከህፃኑ ሰውነት ውስጥ የሚወጣውን ፈሳሽ በመተካት ህፃኑ ቶሎ እንዲያገግምና ጉልበት እንዲያገኝ እንዲሁም የምግብ ፍላጐቱ እንዲመለስ ከማድረጉም በላይ ለቀጣዮቹ 2 እና 3 ወራት በተቅማጥ በሽታ እንዳይያዝ ለማድረግ እንደሚያስችልም ተገልጿል፡፡ በተቅማጥ በሽታ የተያዘ ህፃን 10 ፍሬ ዚንክ ከህይወት አድን ንጥረ ነገር (ORS) ጋር መውሰድ እንዳለበትም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡
መድሃኒቱ ከቀጣዩ ወር ጀምሮ በየፋርማሲውና በየጤና ተቋማቱ ውስጥ በስፋት እንዲዳረስ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።  

Published in ዜና
Monday, 10 February 2014 08:02

አያዎ NGOር አያዎ ከሰል

“ውቅያኖሱ በተቃርኖ የተሞላ ነው”
“ውቅያኖሱ በተቃርኖ የተሞላ ነው” ብዙ አይነት ከሰል አለ… የድንጋይ ከሰል፣ የእንጨት ከሰል፣ የመተሃራ ከሰል፣ የሺሻ ከሰል፣ የሟክ ከሰል ወ.ዘ.ተ. (ወሳኙን ዘርዝሬ ተውኩት)… እና ደግሞ… ይሄኛው ከሰል፡፡ እኔ የማወራው ስለዚህኛው ከሰል ነው፡፡ ‘አያዎ ከሰል’ ብዬ ስለሰየምኩት - የተቃርኖ ከሰል፡፡ “ውቅያኖሱ በተቃርኖዎች የተሞላ ነው!” አለች አሜሪካዊቷ የስነ - ምህዳር ተመራማሪ ራቼል ካርሰን፡፡ ሴትዮዋ ይሄን ያለችው፣ ለአመታት በአካባቢ ጥበቃ መስክ ያደረገችውን ጥናት መነሻ በማድረግ፣ በውሃ አካላት ውስጥ ስላለው ህይወት በAtlantic Monthly መጽሄት ላይ በከተበችው ጽሁፏ ነው፡፡ ራቼል ካርሰን፤ ከውሃው ውስጥ አለም ያየችውን ብታይ ነው እንግዲህ ይህን ማለቷ፡፡ እኔም የውቅያኖሱን በተቃርኖ መሞላት ለመመስከር፣ እንደ ራቼል ካርሰን በአካባቢ ጥበቃ መስክ ጥናት ማድረግ ግድ አይለኝም፡፡ በአካባቢ ጥበቃ መስክ ከሚሰራ የአንድ ሎካል NGO ሰራተኞች ጋር መዋል ይበቃኛል፡፡ ከእነሱ ጋር ዋልኩ… ዋልኩና ያየሁትን አየሁ… አየሁናም እንዲህ አልኩ… “እርግጥ ነው!... ውቅያኖሱ በተቃርኖዎች የተሞላ ነው!” ይሄን ያልኩት ከ‘አያዎ ከሰል’ በመነሳት ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም…. በረሃማነትን ለመከላከል ከሚሰራው NGO ጋር ወደ ወለጋ፣ ነቀምት ሄድኩ - ለዘገባ፡፡

እርግጥም ድርጅቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከደን ጭፍጨፋ እንዲታቀብ በማድረግ በኩል ሰፊ ስራ ሰርቷል፡፡ ነዋሪዎች ዛፍ መቁረጥ እየተው ነው፡፡ ችግኝ መትከል እያዘወተሩ ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ግን አንዳንድ የግንዛቤ ለውጥ ያላመጡ ዛፍ ነቃዮችና ከሰል አክሳዮች አሉ፡፡ ለእነዚህኞቹ የደን ቀበኞች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፣ NGOው የ3 ቀናት አውደጥናት ያካሄደው፡፡ በደን ሽፋን መቀነስና በበረሃማነት መስፋፋት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደረገ፡፡ በጊምቢ አካባቢ በደን ጥበቃ ረገድ የተከናወኑ መልካም ተሞክሮዎች ቀረቡ፡፡ ከሰል ከማክሰል ህገ ወጥ ድርጊታቸው ታቅበው፣ በመደራጀት ምድጃ ማምረት የጀመሩ 7 ሰዎች ልምዳቸውን አጋሩ፡፡ የ NGOው የደን እንክብካቤ ኤክስፐርት፤የከሰል ማክሰልንና የበረሃማነትን ግንኙነት የሚያሳይ፣ የመፍትሄ ሃሳብ የሚሰነዝር 33 ገጽ የዳሰሳ ጥናት በፓዎር ፖይንት አቀረቡ፡፡ በጥናቱ ዙሪያ ውይይት ተደረገ፡፡

ቀጣይ የድርጊት መርሃግብር ተቀረጸ፡፡ ብዙ ነገር ተደረገ… አውደ ጥናቱ በስኬታማ ሁኔታ ተጠናቀቀና በመጣንባት አነስተኛ አውቶብስ ተሳፍረን ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመርን፡፡ መንገድ ላይ በ NGOው ሶስት ሰራተኞች መካከል ውዝግብ ተፈጠረ፡፡ የውዝግቡ ሰበብ ከላይ የጠቀስኩት ‘አያዎ ከሰል’ ነው፡፡ “እንግዲህ ተስማሙ!... ጊቤ በረሃ ኬላ ላይ ያሉት ጠባቂዎች፣ ከ 1 ከሰል በላይ አያሳልፉም!...” አለ ሾፌሩ ቢጨንቀው፡፡ “ለቤት አከራዪ ሁለት ኩንታል ከሰል አመጣልዎታለሁ ብያቸዋለሁ… እኔ ነኝ የምጭነው” አለ አንደኛው፡፡ “ለቤት አከራዪ ትላለህ እንዴ!?... እኔ‘ኮ ለሚስቴ ቃል ገብቼላታለሁ!...” ብሎ ተሟገተ ሌላኛው፡፡ “ለሾፌሩ ገና ከአዲሳባ ሳንነሳ ነው፣ 2 ከሰል እንደምጭን የነገርኩት!... ከፈለጋችሁ ጠይቁት!” ብላ ምስክር ጠራች 3ኛዋ፡፡ ጭቅጭቁ ቀጠለ… እኔ በግርምት የሚሆነውን አያለሁ… የሶስት ቀኑን አውደጥናትና የአሁኑን ውዝግብ አሰላስላለሁ… “አያዎ NGO!!!… አያዎ ከሰል!!!...” እላለሁ፡፡ በነጋታው ዜና እሰራለሁ… “በረሃማነትን ለመከላከል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ” የሚል ርዕስ ያለው ዜና!! “ውቅያኖሱ በተቃርኖዎች የተሞላ ነው!”

Published in ባህል

          በአምቦ እርሻ ኮሌጅ በማታው ክፍለ ጊዜ እየተማሩ በእርሻ ሙያ በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ፣ የእርሻ መምህር ሆኑ፡፡ በዚህ ሙያ ለ25 ዓመታት ከልብ ቢያስተምሩም ጠብ ያለ ነገር አላዩም፡፡ ክፍል ውስጥ በንድፈ ሐሳብ (ቲዎሪ) የሚያስተምሩትና በተግባር የሚሰራው በፍፁም አይገናኙም፡፡ እርሻ ያስተማሯቸው ተማሪዎች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ የአካባቢው ሕዝብ፣ አገሩ በሙሉ በንድፈ ሐሳብ የተማረውን ወደ ተግባር አይለውጥም፡፡ በዚህም በጣም ተናደዱ፡፡
“የማስተምረውን ልስራ፣ የምሰራውን ላስተምር” በማለት መሬት ጠየቁ፡፡ በዚያን ጊዜ አገሪቷ የምታራምደው ርዕዮተ-ዓለም ሶሻሊዝም ስለነበር፣ መሬት ሊሰጣቸው ቀርቶ ጥያቄያቸውንም ያዳመጠ አልነበረም፡፡ ሐሳባቸውን ለማሳካት ያደረጉት ጥረት ቢከሽፍም በ1967 ዓ.ም ለቤተሰብ ወተት ብለው የገዟት ላም፣ ዛሬ ተራብታ  ሚሊዮን ብሮች ማፍራቷን አቶ ጋዲሳ ጎበና ይናገራሉ፡፡
ብዙ ጊዜ የሕግ ባለሙያዎች፣ ሐኪሞች፣ ነርሶች .. ካልሆኑ በስተቀር፣ ቢዝነስም ሆነ ሳይንስ (ባይሎጂ፣ ኬሚስትሪ)፣ ሒሳብ፣ እርሻ፣ …የሚያስተምሩ መምህራን በንድፈ ሐሳብ የሚሰጡትን ትምህርት ወደተግባር ለውጠው፣ ሕይወታቸውን አሻሽለው ኑሮአቸውን ሲቀይሩ አይታዩም፡፡ በዚህ ረገድ አቶ ጋዲሳ፣ ታላቅ የምሁር አርአያ (ሞዴል) ናቸው፡፡
በ1967 ዓ.ም ኢትዮጵያ የነበረችበት ሁኔታ ይታያችሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ቢዝነስ፣ የግል ኢንቨስትመንት፣ ሕይወት ማሻሻልና ኑሮን መለወጥ፣ … የሚባሉ ነገሮች አይታሰቡም፡፡ የሶሻሊዝም ጸር ስለሆኑ ውጉዝ ናቸው፡፡ ያሰበ፣ ያሳሰበ፣ … በሚል ሕይወትን የሚያሳጣ ቅጣት ሊጣልበት ሁሉ ይችላል። በዚያን ጊዜ በነበረው አስተሳሰብ “የማስተምረውን ልስራ፣ የምሰራውን ላስተምር” ብሎ መነሳት ታላቅ ብስለት፣ አስተዋይነትና ምጥቀት የሚያሳይ ከፍተኛ ድፍረት ነው፡፡
ለመሆኑ አቶ ጋዲሳ ጎበና ማናቸው? ምሁሩ ኢንቨስተር፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን በቀድሞው አጠራር በሆሮጉድሩ አውራጃ አቤደንገሮ ወረዳ ገበር በተባለ ልዩ ስፍራ ከገበሬ ቤተሰብ የተወለዱ ሰው ናቸው፡፡ አንደኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሻምቡ ት/ቤት አጠናቅቀው፣ 2ኛ ደረጃን በአምቦ ማዕረገ ሕይወት ት/ቤት እስከ 10ኛ ክፍል ተከታተሉ፡፡ ከዚያም በ1962 ዓ.ም ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ገብተው፤ ሁለት ዓመት የመምህርነት ኮርስ ተከታትለው በዲፕሎማ ተመረቁ፡፡ ውጤታቸው ጥሩ ስለነበር በቀጣዩ ዓመት እዚያው ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ሞዴል አንድ ት/ቤት እንዲያስተምሩ አስቀሯቸው፡፡ እዚያ ከአንድ ዓመት በላይ አልቆዩም፡፡ ትምህርታቸውን ለማሻሻል በነበራቸው ፍላጎት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው፣  በኤጁኬሽን በዲፕሎማ ተመረቁና  ሆሳዕና ተመደቡ፡፡ ከዚያም በአሁኑ ዋቸሞ በቀድሞው ልጅ አበበ ት/ቤት አስተማሩ፡፡
ሆሳዕናም አልቆዩም፡፡ በ1966 ዓ.ም ወደ ተማሩበት አምቦ ማዕረገ ሕይወት 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተዛውረው፣ ለ25 ዓመት በትምህርት ሚ/ር ስር ማገልገላቸውን ተናግረዋል - አቶ ጋዲሳ፡፡ በማታው ክፍለ ጊዜ አምቦ እርሻ ኮሌጅ ተምረውም በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ የእርሻ መምህር ሆኑ፡፡ ለትንሽ ጊዜ ትምህርት ሚ/ር ለቀው ግብርና ሚ/ር ገብተው ነበር፡፡ ያኔ የውጭ አገር የትምህርት ዕድል ሲመጣ ለእሳቸው አይሰጥም፤ ሌሎች ናቸው የሚላኩበት። ይህ አሰራር ያበሳጫቸው ነበር፡፡ “ጥሩ ውጤት ስላለኝ በግሌ ለምን አልሞክርም?” በማለት የነፃ ዕድል ትምህርት ማፈላለግ ጀመሩ፡፡ ኤሊኖይ-አሜሪካ ሻንፔን ዩኒቨርሲቲ ውጤታቸውን አይቶ ስኮላርሽፕ ሰጣቸውና፣ በ1977 ዓ.ም ለትምህርት ወደ አሜሪካ ሄዱ፡፡ በ1980 ዓ.ም በእርሻ አድቫንሲንግ ዲፕሎማ ተቀብለው፣ እዚያው ለሁለት ዓመት ከሰሩ በኋላ ደርግ ከስልጣን ሲወርድ ወደ አገራቸው ተመለሱና መሬት ተሰጥቷቸው ወደ እርሻ ገቡ፡፡
እንዴት ወደ እርሻ ኢንቨስትመንት ገቡ? ማለታችሁ አይቀርም፡፡ እንዴት እንደሆነ ራሳቸው ያጫውቱናል፡፡ እርሻ የተማርኩት ስለምወደው ነው እንጂ ለጥቅም ብዬ አይደለም፡፡ እርሻ ሳስተምር ተማሪው እንዲገባው በጣም እለፋለሁ፣ እደክማለሁ፤ ለፈተና እዘጋጃለሁ፡፡ ነገር ግን እኔ ከመጽሐፍ ላይ የማስተምረው ቲዎሪ በተግባር ሲገለፅ ምንም አይገናኙም፡፡ ስለዚህ “የማስተምረውን ልሰራ፣ የምሰራውን ላስተምር” በማለት መሬት ጠየቅሁ። በዚያን ጊዜ የታወጀው የሶሻሊስት አስተዳደር ስለሆነ፣ መሬት ሊሰጠኝ ቀርቶ ያዳመጠኝም አልነበረም፡፡ በዚያ የተነሳ ለቤተሰቤ ወተት ትሆናለች በማለት በ1967 ዓ.ም አንድ ላም ገዛሁ፡፡ ያቺ ላም ጥሩ አያያዝ ስለተደረገላት የምትሰጠው ወተት ጨመረ፣ ከእኛ የተረፈውንም ወተት ለጎረቤቶቻችን እየሸጥን በደስታ ጥሩ መኖር ጀመርን፤ እሷም እየወለደች መርባቱን ቀጠለች፡፡
እንዲህ ጥቅም ካለው ለምን የበለጠ አልሰራበትም? በማለት ግቢ ውስጥ ጥንቸል ማርባት፣ በግ ማድለብ፣ የጓሮ አትክልት መስራት፣ የተወለዱን ጥጆችና ግልገሎች መንከባከቡን ቀጠልኩ፡፡ በዚህ ዓይነት እየሰራሁ ሳለ ቆየሁና፣ አንድ ቀን ንድድ ብሎኝ “የምሰራውና የማስተምረው ካልተገናኘ ከአሁን ጀምሮ እኔ ገበሬ መሆን አለብኝ” ብዬ ወሰንኩ
ጊዜው መቼ ነው?
እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት በ1976 ዓ.ም ነበር፡፡ ግን፣ ያዳመጠኝ ሰው ባለመኖሩ ትቼው በውስጤ ሲብላላ ኖሮ፣ ቅይጥ ኢኮኖሚ ሲታወጅ፣ የመጀመሪያው መሬት ጠያቂ እኔ ነበርኩ፡፡ መሬቱ ቢፈቀድልኝም ስላልተሰጠኝ ስከራከር ኖሬ፣ በ1986 መሬቱ ተለቆልኝ ትክክለኛውን እርባታ ጀመርኩ፡፡
መሬቱ ምን ያህል ነበር?
17.5 ሄክታር መሬት በኢንቨስትመንት ተሰጠኝ፡፡
ስራ ሲጀምሩ ካፒታልዎ ምን ያህል ነበር?
ጥቃቅን ቁሳቁስ እንጂ ምንም አልነበረኝም፡፡ ከባንክ የተበደርኩት 83ሺ ብር ብቻ ነበረኝ፡፡
ምን አስይዘው ተበደሩ?
የጓደኛዬን መኖሪያ ቤት አስይዤ ነው የተበደርኩት፡፡
ብድርዎን ከፈሉ’ዴ ታዲያ?
ወዲያው ነዋ!
በዚያ ገንዘብ ምን መስራት ጀመሩ?
የወተት ከብት ማርባት ጀመርኩ፡፡ የወተቱ ምርት ቶሎ ገንዘብ አላመጣ ሲለኝ፣ ተውኩትና በሬ ገዝቼ እርሻ ጀመርኩ፡፡ የእርሻው ስራ ውጤታማ ሆኖ ብድሬን ቶሎ ስለከፈልኩ ባንክ ትራክተር ገዛልኝ። ትራክተሩ እጄ እንደገባ “ለምን አላስፋፋም?” በማለት መሬት ኮንትራት በመውሰድና መንግስትን በኢንቨስትመንት በመጠየቅ አስፋፋሁት፡፡  
አሁን ምን ያህል መሬት እያለሙ ነው?
ከጓደኞቼ ጋርበጆይንት ቬንቸሩ 500 ሄክታር መሬት አለኝ፡፡ በ15 ዓመት ረዥም ኮንትራት የወሰድኩት 48 ሄክታር፣ የበፊቱ 17.5 ሄክታር አለ፣ በእጄ አልገባም እንጂ መንግስትም በቅርቡ የሚሰጠኝ መሬት አለ፡፡ ብዙ ትራክተሮች እየገዛሁ ስለሆነ መሬት በኮንትራት የሚሰጠኝ ሰው በዝቷል፡፡
ምን ያህል ትራክተር አለዎት?
አራት አለኝ፡፡
ማጨጃና ኮምባይነርስ አለዎት?
የለኝም፡፡ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ብዙ እየባከነ ስለሆነ፣የወደፊት ትልቁ ምኞቴ ኮምባይነር መግዛት ነው፡፡ መውቂያዎች ግን ብዙ አሉኝ፡፡ ዩኤስኤአይዲም አላስረከበኝም እንጂ አንድ መውቂያ ገዝቶልኛል፡፡
ከብት እርባታውን ተውት እንዴ?
ለምን እተዋለሁ? እንዲያውም የጊደር እርባታ (ranch) ጀምሬያለሁ፡፡ ቅድም ያያችኋቸውን ዓይነት ጊደሮች እያባዛው እሸጣለሁ፡፡
እንዴት ነው የሚያባዙት?
ቀለብ እንሰጣቸዋለን፣ ይጠቃሉ፣ የስድስትና ሰባት ወር ክበድ (እርጉዝ) ሲሆኑ ይሸጣሉ፡፡ አሁን የእኛን ጊደሮች ፈላጊ በዝቷል፡፡
አንድ ጊደር ምን ያህል ይሸጣሉ?
ሌሎች ከ30 እስከ 35 ሺ ብር ይጠይቃሉ፡፡ እኔ ከዚያ በላይ ነው የምጠይቀው፡፡
ስንት?
ልትገዛ ስትመጣ ነው የምነግርህ እንጂ የተወሰነ ዋጋ የለም፡፡
ስንት ጊደሮች አልዎት?
ከ30 እስከ 40 ይሆናሉ፡፡
ወተትስ የለዎትም እንዴ?
ለዚህ ከተማ የምናከፋፍለው እኛ አይደለንም እንዴ? ቅድምስ ጠጡ ብዬ ያመጣሁት ከየት መሰለህ? ከእርሻዬ ኮ ነው፡፡
ለዚህ ከተማ በቀን ምን ያህል ሊትር ያከፋፍላሉ?
በቀን ከ 300 እስከ 400 ሊትር፣ ከዚያም በላይ ሊሄድ ይችላል፡፡
የሚታለቡ ላሞች ምን ያህል ናቸው?
እርግጠኛ አይደለሁም፤ ከ50 እስከ 60 ሊደርሱ ይችላሉ፡፡
እርሻው ምንድነው የሚያመርተው?
የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የሽንብራ፣ የባቄላ፣ የበቆሎ… ምርጥ ዘር እናመርታለን፡፡ በቆሎ፣ ስንዴ፣ … ስል አንድ ዓይነት ብቻ አይደለም፡፡ አራት አምስት ስድስት ዓይነት ነው፡፡ ለምሳ ያዘጋጀነው እንጀራ እንኳ ሁለት ዓይነት ነው፤ አንዱ ቢጫ አንዱ ነጭ ነው፡፡ ሽንብራም የምናመርተው አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ሽንብራ፣ ስንዴ፣ … ለቆላ፣ ለደጋ፣ ለወይና ደጋ እያልን ነው የምናመርተው፡፡
ምርጥ ዘር ታዘጋጃላችሁ እንዴ?
እኛ’ኮ ምርጥ ዘር አምራች ነን፡፡ እኛ ተራ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ … አናመርትም፡፡ ሁሉም ምርጥ ዘር ነው፡፡ መስራች ዘሩን ከመንግስት ገዝተን ዘሩን አባዝተን፣ ምርጥ ዘር መሆኑ ተረጋግጦ፣ ታግ ለጥፈን ነው የምንሸጠው፡፡
ከወተት ላሞች ውጭ የሚያረቡት ዝርያ አለ?
በቅርቡ የቡፋሎ ዝርያ (ጎሽ መሳይ እንስሳ) ከሕንድ አስመጥቼ በግቤ ሸለቆ ውስጥ ለማርባት ተነጋግሬአለሁ፡፡ የእኛ ሰው ጎሽ ስለገደለ ይፎክራል፣ ይሸልላል፣ ይቀባል፡፡ ጦር ወርውሮ ከብቱ ኃይለኛ ስለሆነና ሊገድለው ስለሚችል ቢፎክር ምንም አይደለም፡፡ በጥይት ተኩሶ በሚገደልበት ዘመን መፎከር ትርጉም የለውም፡፡ ቡፋሎ ወይም ጎሽ ለማዳና የዋህ እንስሳ ነው፡፡ የእኛ አገሩ እንደ ሜዳ አህያ ኃይለኛ ስለሆነ አልተጠጋነውም፡፡ የኤስያው ግን ከፍተኛ ወተትና ቅቤ ነው የሚሰጠው፡፡ የሚፈልገው ረግረጋማ ስፍራ ሄዶ ውሃውን ከጠጣ በኋላ ሲተኛ ነው የሚውለው፡፡ ስለዚህ ዘሩን (ሲመኑን) አምጥቼ ከሌሎች ከብቶች ጋር ለማዳቀል እየተነጋገርኩ ነው፡፡
 ይህን እንስሳ ማርባት ለምን ፈለጉ?
ዋተር ቡፋሎ መኖር የሚፈልገው ውሃ ባለበት ረግረጋማ ስፍራ መሆኑ፣ ሁለተኛ ከፍተኛ ምርት መስጠቱ፣ ሶስተኛ ይህ እንስሳ አውሬ ያለመሆኑን እንዲያውቁና አውሬ የሆነ እንዳለ ሁሉ ለማዳም አለ ለማለት ነው፡፡
ከውጭ አገራት የቀሰሙት ነገር አለ?
አዎ! ሙያዬን በተመለከተ በዘር ብዜት ቱርክ፣ ቻይና፣ ኢጣሊያ፣ ጃፓን፣ አፍሪካም ውስጥ ብዙ አገሮች ሄጃለሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት ቱኒዝ ነበርኩ፡፡ አሁን ደግሞ ቤኒን እሄዳለሁ፡፡
የንብ እርባታ? አላቸው ሲባል ሰምቼ ነበር፡፡ እንዴት ነው?
አዎን! 40 ዘመናዊ ና ከ100 በላይ የሽግግር ቀፎዎች አሉኝ፡፡ ባህላዊ ቀፎ ደግሞ ብዙ ነው ለቁጥርም ይከብዳል፡፡ የማር ማቀነባበሪያ ስላለን እያሸግን እናቀርባለን፡፡
የጓሮ አትክልት አያመርቱም?
አለ! ግን መጠነኛ ነው፡፡ እኛ ለከብቶች መኖና ገፈራ፣ በብዛት የምናመርተው በቆሎ ነው፡፡ እሸቱን ለገበያ እናቀርባለን፣ ተረፈ-ምርቱን ደግሞ ገፈራና ለከብቶች መኖ እናደርጋለን፡፡
ገፈራ ምንድነው?
ገፈራ የሚባለው የበቆሎው ቅጠል ሳይደርቅ ከእህሉ ጋር ታምቆ ለወተትና ለሥጋ ከብት የሚቀርብ ምግብ ነው፡፡
ከዩኤስ ኤ አይዲ ጋር ምን እየሰራችሁ ነው?
ከዚህ ድርጅት ጋር የምንሰራው የእርሻ ምርት ግብአት አቅርቦትና ስርጭት ነው፡፡ እነሱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች አጠቃቀምና አያያዝ… የአቅም ግንባታ ስልጠና ይሰጡናል፤ እኛ ደግሞ ገበሬውን እናሰለጥናለን፡፡ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ገበሬው ይህን የአቅም ግንባታ ካገኘ፣ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ፅረ-አረምና ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች፣ የእንስሳት መድኃኒት፣ … በአግባቡ ከተጠቀመ ምርቱ ይበዛል፣ ገቢው ይጨምራል፣ ኑሮው ይሻሻላል። ገበሬው ምርቱ እንዳይጨምር ማነቆ የሆነበት እነዚህን የምርት ግብአቶች ያለማግኘት ነው፡፡ እኛ እነዚህን ግብአቶች በአንድ ስፍራ እናቀርባለን፡፡ ስለ አጠቃቀምና ጥንቃቄያቸውም እናስተምራለን፡፡ ዩኤስ ኤ አይ ዲ የቴክኒክና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋል፤ ለጥቂት ባለሙያዎች ደግሞ ደሞዝ ይከፍላል፡፡ ከዚህ ውጪ በጥሬ ገንዘብ የሚሰጠን ነገር የለም፡፡ የምርት ግብአቶቹን የማቀርበው እኔ ነኝ፡፡
ብዙ የተማረ ሰው በእርሻው ዘርፍ ሲሰማራ አይታይም፡፡ ችግሩ ምንድነው?
በጣም ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ዋነኞቹ ችግሮች መሬትና ፋይናንስ ናቸው፡፡ የመሬት አቅርቦት የለም። መሬት የምታገኘው ብዙ ተቸግረህ፣ ብዙ ከስረህና ፍዳህን አይተህ ነው፡፡ የተማረ ሰው፣ እውቀት እንጂ ገንዘብ የለውም፡፡ እርሻ ደግሞ ዳጎስ ያለ ካፒታል ይፈልጋል፡፡ ሌላው ችግር፣ “ያለኝን ጥሪት እርሻ ላይ አፍስሼ ውጤታማ ባልሆንስ?” የሚለው ስጋትና ፍርሃት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት፣ በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል ሲያቅድ እነዚህ ቁልፍ ችግሮች የሚወገዱበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል። ተፈጥሯዊ የሆኑት ድርቅና ከመጠን ያለፈ ዝናም፣ ገበያ እጦት፣ ተባይ፣ … ሌሎች ችግሮች ናቸው፡፡
እርስዎ፣ በ20 ዓመት የእርሻ እንቅስቃሴ ውስጥ እጅግ ፈታኝ ነበር፤ ግን ተወጣሁት ወይም አሁንም በስራዬ ላይ እንቅፋት ሆኖ እየፈተነኝ ነው የሚሉት ችግር አለ?
አለ እንጂ! እኔ በርካታ እልህ አስጨራሽ ችግሮች ገጥመውኝ ተወጥቻቸዋለሁ፡፡ ነገር ግን እንደመብራት እጅግ የፈተነኝ ችግር አላጋጠመኝም። የመኖ ማቀነባበሪያና የዘር ማበጠሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም፣ መብራት እንዲገባልኝ ለኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን የአምቦ ጽ/ቤት 176ሺ ብር የከፈልኩት በ2003 ዓ.ም ነበር፡፡ ገንዘብ ስከፍል ኮርፖሬሽኑ የተሰጠኝ ማስረጃ “አንድ ደንበኛ ገንዘብ ከከፈለ 7 ቀን በኋላ ይገባለታል” ይላል፡፡ ከ 7 ቀን በላይ ይኼው 4 ዓመት ተቆጠረ፡፡
ገንዘብ እንደከፈልኩ መስመር ዘረጉ፣ ትራንስፎርመር ተከሉ፡፡ ፋብሪካዎቹ የሚተከሉበት ሕንፃ ከተሰራ አራት ዓመት ጨርሷል፡፡ የውሃ ጉድጓድ ለማስቆፈር ጨረታ አውጥተን ለአሸናፊው 700ሺ ብር ከፍለን፣ በ165ሺ ብር ኬብል ገዝተን ጉድጓድ ውስጥ ከገባ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ መሳሪያዎቹ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከልማት ባንክ ከተገዙ አራት ዓመት ስላለፋቸው ለብልሽት ተዳርገዋል፡፡ ይህ ችግር እንዲወገድልኝ ያልደረስኩበት መ/ቤት የለም፤ ኢንቨስትመንት ጽ/ቤትም ያውቃል፡፡
ሲጠይቋቸው ምንድነው የሚሰጡዎት ምላሽ?
ሙስና አለባቸው፡፡ ከእኔ በኋላ ለስድስት ሰው ትራንስፎርመር ተክለው አስገብተዋል፡፡ እኔ ሕጋዊ ሰው ስለሆንኩ ያለደረሰኝ 5 ሳንቲም አልሰጥም። ለማን አቤት! ማለት እንዳለብኝ ግራገብቶኝ ተቀምጫለሁ በማለት አቶ ጋዲሳ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡

የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ4ኛ ዙር 2010-2011 እና 2014-2015 ባወጣው የጤና አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮግራም እንደ ዋና ግቦች ከሚቆጠሩት መካከል፡-
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ከ25% ወደ 60% ማሳደግ፣
በጤና ተቋማት እና በሰለጠነ የሰው ኃይል የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ከ12%-32% ማሳደግ፣
የተሟላ ጤንነት ያላቸውን ልጆች ቁጥር ከ45% ወደ 80% ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የኢትዮያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ2010-11 እና 2014-15 ባወጣው የጤና አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮግራም በተጨማሪ እንደተጠቆመው  በአሁኑ ወቅት
በኢትዮጵያ የእርግዝና ክትትል ወደ 68% የደረሰ ሲሆን ከወሊድ በሁዋላ ደግሞ የሚኖረው የህክምና ክትትል ወደ 34% ደርሶአል፡፡  
በኢትዮጵያ በሰለጠነ የሰው ኃይል የመውለድ ልምድ በየጊዜው ቁጥሩ መጨመሩን ብሔራዊው ፕሮግራም ይገልጻል፡፡ ይህም ወደ 18.4% ከፍ እንዳለ ያሳያል፡፡ በእርግጥ ይህ መረጃ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ ለምሳሌም በቤንሻንጉል ጉሙዝ 5.6% ያህል ሲሆን በአዲስ አበባ ደግሞ 62.5% ተመዝግቦአል። በተጨማሪም በአምስት መስተዳድሮች ማለትም በአዲስ አበባ፣ ሐራሪ፣ ደቡብ፣ ድሬደዋ፣ ትግራይ ከእቅድ በላይ መፈጸማቸው ተጠቁሞአል፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አብሮአቸው ከሚሰራቸው ድርጅቶች መካከል WATCH  የተሰኘው አጋር ድርጅት አላማ የእናቶች እና ጨቅላ ሕጻናቶቻቸው ጤንነት እንዲጠበቅና ሞት እንዲቀንስ ማድረግ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት እትም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መስተዳድር ያለውን እንቅስቃሴ ለንባብ ማለታችን ይታወሳል፡፡  ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ክልል መስተዳድሮች፡-
ምን ያህል የጤና አመራሮች ስልጠና አገኙ?
ምን ያህል የጤና ባለሙያዎች ስልጠና አገኙ?
የህክምና መሳሪያዎች ምን ያህል ተሟልተዋል?
የጤና ባለሙያዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ዘልቀው እንዲያስተምሩ ምን ተመቻችቶአል?
የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ቢንያም ጌታቸው አቅርበናል፡፡
ጥ/ WARCH  የት የት አካባቢዎች ይሰራል?
WARCH  ማለት women & their children health first  ማለት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ቅድሚያ ለእናቶችና ልጆቻቸው ጤንነት የሚል መርህ ያለው ሲሆን በኢትዮጵያም ውስጥ በሶስት መስተዳድሮች ተግባሩ እንዲከናወን ሁኔታዎችን አመቻችቶአል፡፡ ፕሮጀክቱ በደቡብ በሲዳማ ዞን በሶስት ወረዳዎች፣ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ  ዞን በሶስት ወረዳዎች እና በጅማ በሁለት ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮጀክት የሚተገበረው ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በተጨማሪ በዋናነት በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ አማካኝት ነው፡፡
ጥ/ ፕሮጀክቱ በሚከናወንባቸው ክልሎች ምን ያህል የጤና አመራሮቸች ሰለጠኑ?
መ/ WARCH  በሚሰራባቸው ሶስት ክልላዊ መስተዳድሮች ከጤና ባለሙያዎቹ አስቀድሞ ወደ 85/የሚሆኑ የጤና አመራሮች ስለፕሮጀክቱ ማለትም የእናቶችንና ህጻናትን ሞትን ለመቀነስ በሚደረገው እንቅስቃሴ እውቀቱ እንዲኖራቸው የማነቃቂያ ስልጠና ወይም አውደጥናት ለሶስት ቀናት ያህል ተካሂዶአል፡፡ በዚያም ላይ የዞን ጤና መምሪያ ኃላፊዎች፣ የወረዳ ጤና አመራሮች፣ የጤና ጣቢያ አመራሮች እና ከክልል ጤና ቢሮ በማቀናጀት ነበር የተሳተፉት፡፡ በወቅቱም ሁሉም ተሳታፊዎች ወደቢሮአቸው ሲመለሱ ምን መስራት እንዳለባቸው እቅድ አውጥተው የተለያዩ ስለሆነ በዚያው መሰረት ይተገብራሉ የሚል እምነት አለን፡፡
ጥ/   በሶስቱም ክልሎች ምን ያህል የጤና ባለሙያዎች ሰለጠኑ?
መ/ በሶስቱም ክልል መስተዳድሮች ለ146/ ጤና ባለሙያዎች የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናቱን እንክብካቤ ለመተግበር የሚያስችለው Basic emergency obstetric & newborn care የተሰኘው ስልጠና ተሰጥቶአል። እነዚህ ባለሙያዎች ለስምንት ቀን የቃል ትምህርቱን ከወሰዱ በሁዋላ ለአስር ቀናት ደግሞ የተግባር ስልጠና ስለሚሰጣቸው ቀደም ሲል በሚያውቁት የህክምና አሰራር ላይ ተጨማሪ እና በቂ ልምድን በመቅሰም እናቶችን በየጤና ጣቢያው በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ያስችላል ተብሎ ይገመታል፡፡
ጥ/ የጤና ባለሙያዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ዘንድ ደርሰው እንዲሰሩ ምን ተመቻችቶአል?
መ/ ወላዶች ወደ ጤና ጣቢያ የማይመጡባቸው ምክንያቶች በጥናት እንደተረጋገጠው ከሆነ     ሶስት ናቸው፡፡  እነርሱም ሶስቱ መዘግየቶች በሚል ይታወቃሉ።
እናቶች ወደጤና ተቋም ሄደው በአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው ግንዛቤው ሳይኖራቸው፣
በጤና ተቋም መውለዳቸው ጠቃሚ እንደሆነ ቢያውቁትም ነገር ግን የመጉዋጉዋዣ እና ጥረት ወይንም የገንዘብ እጦት በመሳሰለው ሁኔታ መጠቀም ሳይችሉ ሲቀሩ፣
ወደም ጤና ተቋም ቢሄዱም በዚያ ባለው የአገልግሎት አናሳነት ምክንያት መጠቀም ሳይችሉ ሲቀሩ ነው፡፡
ከዚህ ውጭ ግን የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሮጀክቱን ሲተገብር በየክልል መስተዳድሩ ካሉ አገር በቀል ድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በመተባበር በጥናት የተገለጹትን መዘግየቶች ለማስወገድ በሚያስችል መንገድ የተቀናጀ አሰራር ተዘርግቶአል፡፡ ወደህብረተሰቡ ዘንድ በመውረድ ህብረተሰቡ ወደጤና ተቋም በመሄድ ግልጋሎት የማግኘት ልምድን እንዲያዳብር እና አስቀድሞውኑ ዝግጁነት እንዲኖር የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስልጠናው ለጤና ባለሙያዎች በሚሰጥበት ወቅት ባለሙያዎችን የማነሳሳት ስራ ይሰራል፡፡ በዚህም ረገድ ህብረተሰቡ ወደጤና ተቋም በማይመጣበት ጊዜ በጤና ተቋም ቁጭ ብለው እንዳይጠብቁና ወደጤና ኬላ በመሄድ እንዲሁም ከጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ጋር በቅርብ በመገናኘት ህብረተሰቡን እንዲያነቃቁ ይመከራል፡፡
“...በአማራ ክልል የተገኘ አንድ ተሞክሮ እንደሚያሳየው  የጤና ባለሙያዎቹ ሰልጥነው ወደየጤናጣቢያቸው ሲመለሱ ታካሚዎችን እንደተጠበቀው ማግኘት አልቻሉም፡፡ ስለዚህም ባለሙያዎቹ ወደጤና ኬላዎች በመውረድ ከጤና አክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር በመሆን በየቀበሌው ያሉ እርጉዝ እናቶችን በመመዝገብ፣ የመውለጃ ጊዜያቸውን በመለየት፣ እግር ተግር እየተከታተሉ እና ምክር እየሰጡ ወደጤና ተቋም እየሄዱ እንዲወልዱ አድርገዋል፡፡ በዚህም አሰራር አርግዘው የነበሩ  እናቶች  በአብዛኛው በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በጤና ተቋም እንዲወ ልዱ አስችሎአል፡፡”
ጥ/ የእናቶችንና ጨቅላ ሕጻናቱን ጤና ለመጠበቅ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች የመሳሪያ እጥረት ቢገጥማቸው በምን መልክ ችግሩ ይፈታል?
መ/ በእርግጥ በጤና ጣብያዎቹ ያለውን አሰራር ለማወቅ እና ድጋፍ ለማድረግ በየተወሰነ ወቅት ጉብኝት ይደረጋል። ጉብኝቱም የሚከናወነው በጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ሲሆን ጉድለት ናቸው የሚባሉት ነገሮች በሙሉ ይመዘገባሉ፡፡ ለምሳሌ ...የህጻናት እስትንፋስ መስጫ ስለማያገኙ ለአዋቂ በሚሆን መሳሪያ ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡ ይህንን መሳሪያ በሚጠቀሙ ጊዜ ምናልባት ጥንቃቄ የጎደለው ከሆነ ሕጻናቱን ከአደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ጉድለቶችን በእርግጥ ጊዜ ሳይሰጡ ማስተካከል ያስፈ ልጋል፡፡ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመሆን በፕሮጀክቱ ስር የታቀፉትን 48/የጤና ጣብያዎች አቅም የሚመለከት የዳሰሳ ስራ ተሰርቶ በፕላን ኢንተርናሽናል በኩል የጎደሉ እቃዎች በተወሰነ ደረጃ እንዲሟሉ ተደርጎአል፡፡ በእርግጥ ለሁሉም ጤና ተቋማት በአንድ ጊዜ ማሟላት ስለማይቻል በሁለተኛው ግዢ ደግሞ ለተቀሩት ይዳረሳል ብለን እንገምታለን። ከዚህም ጎን ለጎን መንግስትም የጤና ጣብያዎቹን አቅም ለማጎልበት አስፈላጊውን በማድረግ ላይ ስለሆነ በዚህ መልክ በተቀናጀ ሁኔታ አገልግሎቱን ለእናቶችና ለጨቅላዎቻቸው በተገቢው ለማዳረስ ጥረት ይደረጋል፡፡
ጥ/ ፕሮጀክቶቹ በሚተገበሩባቸው መስተዳድሮች ስልጠና ያገኙ የጤና አመራሮቹ ምላሽ ምን ይመስላል?
መ/ በእርግጥ በሁሉም ወረዳዎች ያሉ አመራሮች አንድ አይነት እንቅስቃሴ አያሳዩም፡፡ አንዳንዶች ከሚገባቸው በላይ ወርደው እያንዳንዱን ስራ ሲከታተሉ አንዳንዶች ደግሞ የመቀዛቀዝ ሁኔታ ይታይታባቸዋል፡፡ በእርግጥ ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም በስራ ዝውውር ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ለዚህ እንደመፍትሔ የተቀመጠው ከአንድ ወር በሁዋላ ቀድሞ የሰለጠኑትንም አሁን በስራው ላይ ያሉትንም በመሰብሰብ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ  የማነቃቂያ አውደጥናቱን እደገና ለመስጠት እቅድ ተይዞ አል፡፡ ይህ የእናቶችና ጨቅላ ሕጻናቶቻቸውን ጤና የመጠበቅ ስራ የፕሮጀክቱ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሀገር እንዲሁም የአለም ትኩረት በመሆኑ የሁሉንም ትኩረት ሊያገኝ ይገባል፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

        “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስምንተኛው ሺህ እየተባልን የምንበረግግበት አፈ - ታሪክ፣ አሁን አሁን እየመሰለን  ልባችን መበርገግ ጀምሯል፡፡ በሰው ልጅ ሕሊናዊ መመዘኛዎች ነውርና ፀያፍ የተባሉ ነገሮች እንደጨዋነት አደባባይ ላይ ሰንደቅ ሆነው ወደ መውለብለብ መድረሳቸው፣ሥጋታችንን እጥፍ ድርብ እያደረገው መጥቷል፡፡ ስለዚህም ፊታችን ተጋርጦ ነፃ ትግል ከገጠመን ድህነት ባልተናነሰ  የሞራል ውድቀት፣ የነውር ጫና እያንገዳገደን ነው፡፡
አንዳንድ ዘመኑ ያልዋጣቸው የኪነ-ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ ከዚህ የአገር ክሥረትና ውድቀት ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘው እየተናነቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባለፈው ሰሞን ለአደጋ የተጋለጠውን የወጣቱን ሥነምግባር በተመለከተ ምሁራንንና የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች  ሰብስቦ “ምን ይሻላል?” ሲል አወያይቷል፡፡ ደስ ይላል፡፡ ዛሬ ከእንጀራ ባሻገር የነገን ትውልድ ማሰብ፣ የተቆፈረው ጉድጓድ ዝቅ ሳይል መድፈን፣ ሀገሩንና ወገኑን ከሚወድ ሰው ሁሉ የሚጠበቅ ነው፡፡
ይሄ ሁሉ መንደርደርያ  “የበዓል እንግዶች” የተሰኘውን የዘካሪያስ ብርሃኑን ቴአትር ለመዳሰስ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡ ቴአትሩ በእጅጉ የሚያዝናናና፣ የበሰሉ  ተዋናዮችን ያሳተፈ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ግን እኔን በእጅጉ የመሰጠኝ  ጭብጡ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የልቤን ሃሳብ ያወጣልኝ ቴአትር ብል አላጋነንኩም፡፡
ቴአትሩን በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ካየሁት ውሎ አድሯል፡፡ በመድረክ ላይ የፈሰሰው የዘመናችን የሕይወት ወንዝ ይዞት የሚፈስሰውን ግሣንግስ ሣይ፣ ቁስላችንን እያከከው፣ ደማችንን-እያናወጠው እንደሆነ ተሠምቶኛል፡፡ “ወዴት እየሄድን ነው?” የሚለውን - ጥያቄ በፍጥነት ለመመለስ መታጠቅ እንዳለብን አባንኖናል፡፡
“የበዓል እንግዶች” የታደሙበት ያ - ቴአትር፣ የሮጡበት የቅሌት ሜዳ ሁሉ የነገን መራራ ድጥናማጥ የሚጠቁም ነው፡፡
ቴአትሩ  ያነጣጠረው ለባህር ማዶ ኑሮ ልባቸው ያኮበኮበና ክብረ ሕሊናቸውን የጣሉ የዘመናችን ሰዎች ስግብግብነት ላይ ነው፡፡ ቴአትሩ ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ የሚሽከረከረው ዲያስፖራ ባልና ሚስት ለማግኘት በሚቅበዘበዙ ገፀ ባህሪያት ነው፡፡ አርቲስት ተስፉ ብርሃኔ  የሚጫወተው መርሻ የተባለ ገፀ ባህሪ ከአሜሪካ የሚመጡ ወንዶችን የሚደልልና በዶላር ጥማት የሰከረ ነው፡፡ ደላላው መርሻ እህቱን እሌኒን ያለ ክፍያ ዳያስፖራ ባል ስላጣበሳት አስር ጊዜ ያቅራራል፣ ውለታውን እንደተራራ ይቆልላል። ሌላኛዋ የደላላውን ወንድም ታገቢያለሽ ተብላ የምትጠብቅ ሴት ማለትም ዲቦራ ምናልባትም የቤተሰቦቿን ግፊት ጨምሮ ስለምታገባው ባል ማለትም ጌራወርቅ ጠባይና ሁኔታ እህታቸውን እሌኒን ስትጠይቅ ስናይ፣ የሰው ልጅ ለጥቅም ብሎ ምን ያህል ራሱን እንደጣለ እናስብና እናዝናለን፡፡ እኔ ቴአትሩን ስመለከት ከካናዳ ለመጣ ሰው በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ራስዋን የሸጠች ሴት የደረሰባት አደጋ ነው ትዝ ያለኝ፡፡
እኔ የማውቃት ያቺ የአዲስ አበባዋ ቀልጣፋ፣ ዲያስፖራ በመቀላጠፍዋ  በጊዜው ራስዋን ያደነቀችውን ያህል ሕይወቷን ሙሉ የሚሠቅቅ ሥነ ልቡናዊ ስብራት ተቀብላለች፡፡ ምክንያቱም ያ ሰው የአእምሮ ችግር ያለበት ስለነበር፣ በማታውቀው ሀገር ለጆሮ የሚሰቀጥጡ  ሥቃዮችን አድርሶባታል፡፡ ግን የምርጫዋ ውጤት ስለነበር በማንም ላይ የማዘንና የመፍረድ እድል አላገኘችም፡፡ ይልቁንም በራስዋ ነው የተፀፀተችው፡፡
 የዘካሪያስም ቴአትር የሚናገረው መራራ እውነት ይሄው  ነው፡፡ በዚያው ቤተሰብ ውስጥ የሚታየው የሞራል ውድቀት ወጣቶቹ ላይ ብቻ አይደለም የሚንፀባረቀው፣ ያንን ፀያፍ ድርጊት የምትደግፍ እናትም እናያለን፡፡ እውነት ለመናገር አሁን ባለው ሁኔታ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ወላጆችም “ከአሜሪካ የመጣ ሰው” ሲባሉ መደንበር ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት የኔ የቅርብ ዘመድ የ17 ዓመቷን እምቦቃቅላ ለ56 ዓመት አዛውንት መሸጧን አስታውሳለሁ፡፡ ምክንያቱም አሜሪካ ነዋ! ስለ አሜሪካ ብዙ ብዙ ቢነገርም ሰው አሁንም “አሜሪካ ይግደለኝ”፣ “እዚህ ሰው ከመሆን አሜሪካ ዛፍ መሆን ይሻላል” እያለ ነው፡፡ እርግጥ ነው ዛሬ ኢትዮጵያ ለኑሮ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ መድረሷን አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ ክብርን ሸጦ ፣ ሕሊናን አዋርዶና ትዳርን የሚያህል ከቡር ነገር ሸቅጦ ሰው አገር ለመሰደድ መታተር ያሳዝናልም ያስተዛዝባልም፡፡ የዘካርያስ ብርሃኑ ቴአትር እንደ ሀበሻ እንጀራ ሺህ ዓይን አውጥቶ የጐለጐላቸው ገመናዎችም የዚሁ አካል ናቸው፡፡
በርግጥም ቴአትሩ የኑሯችን ቁራሽ መሆኑን ለመመስከር  በዚህ ሣምንት የገጠመኝን ነገር ብናገር እንኳ  በቂ ነው፡፡ ከሜክሲኮ ወደ ቦሌ በምትጓዘው ታክሲ፣ ከመጨረሻው መቀመጫ ቀደም ባለው ተቀምጬ  ሣለ፣ ከኋላዬ አንዲት ወጣት ሴት ለአንድ ወጣት የምታወራው ወሬ ቀልቤን ሳበው። ልጅቷ ወደ አሜሪካ ለመሄድ በሂደት ላይ መሆንዋን ከንግግርዋ ተረዳሁ፡፡ ቀጥሎ ስታወራ፣ የጠበሰቻቸው ሰውዬ “ሼባ” መሆናቸውን ለልጁ ገለፀችለት፣ ይሁን እንጂ “ሼባው” ቀላል እንዳልሆኑ ነገረችው፡፡ “ጂ ፕላስ ስሪ”  ሠርተዋል፤ ባለ ሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ገዝተዋል፤ ደግሞም በምድር ላይ ብዙ ስለመኖር ሲያወሩ እርሷ ሽምቅቅ ማለትዋን ተረዳሁ፡፡ ዕድሜያቸውን ስታሰላ፣ አሜሪካ ውስጥ 47 ዓመታት ያህል ኖረዋል፤ ከዚህ ሲሄዱ 16 ዓመታቸው ነበር፤ 63 ዓመት ሆኗቸዋል ማለት ነው፡፡
እኔን የገረመኝ ግን ይሄ አይደለም፡፡ “ይበልጥ በጉዳዩ እንድገፋበት የገፋፋኝ ፍቅረኛዬ ነው” ማለቷ እንጂ፡፡ ፍቅረኛውን ለ“ባለሃብት” የሚሸጥ ሆዳም ፍቅረኛ አይገርምም? ምን ያህል እየዘቀጥን እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ሰው የሚያፈቅራትን ሴት፣ ለገንዘብና ለአሜሪካ ብሎ የሚሸጥበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ታዲያ ዘካርያስ ምን ያድርግ? ሀገር እየሞተች፣ ትውልድ በሣቅ ታንኳ እየቀዘፈ - ቁልቁል ወደ መቃብር ሲወርድ፣ ስለ አበቦች ውበት፣ ስለ ወፎች ዜማ ብቻ ያውራ እንዴ? በፍፁም! ይህን ማድረግ የራስን ሥጋ ለመጋጥ ጥርሱን የሚሞርድ ዳይኖሰርን ያህል ጨካኝ መሆን ነው፡፡ ስለዚህ ደራሲው በበዓል እንግዶች” የዘከዘከው እንዲህ ያሉ ነውርና ሀኪም የሚያሻቸው ቅሌቶቻችንን ነው። ስለዚህም ስለሰውየው ማንነትና የጀርባ ሁኔታ ሳናጠና፣ አሜሪካ ሲባል ልባችን የሚቆመውን ሁሉ በጠገበ ጅራፍ ይዠልጠናል፡፡ ልብ ላለው ሰው ልብ የሚሰብር ሃሳብ ነው፡፡ ይህን ልብ የሚሰብር ሃሳብ  በቀልድና ጨዋታ አዋዝቶ ማቅረቡ  ትካዜ እንዳይጨፈጭፈን ያግዛል፡፡ እኔም ልቤ ከንፈርዋን እየመጠጠች ጥርሶቼ እየሣቁ ነበር ቴአትሩን ያየሁት።  
በመሀል በመሀሉም የዘመኑን ፖለቲካና የዳያስፖራዎችን ጭፍን ተቃውሞ ይተቻል - እያዋዛ፡፡ በመንግሥትና ዳያስፖራ ንትርክም ተመልካቹ ይስቃል፣ ያጨበጭባል፡፡ ቴአትሩን ልብ ብሎ ለተከታተለው የዘመናችን ማህበረሰብ  የተንጠለጠለበትን የገደል ዳር ያሳያል፡፡ አንድ ሰው ትዳር ሊይዝ፣ ጐጆ ሊቀልስ ሲነሣ፣ ግራና ቀኙን ጥናት ማድረግ አለበት የሚለውን የሥነ ጋብቻና የሥነ - ልቡና ሳይንስ ምሁራን ሃሳብ አሽቀንጥሮ፣ ለልቅ ወሲባዊ አደጋ መዳረግን እንኳ ሳያስቡ አሜሪካ ብሎ ቀልብ ማጣት፣ የማታ ማታ የሚያመጣውን ጉድ  እሌኒ ከምትባለው ወጣት ገፀ ባህሪ ገጠመኝ መረዳት ይቻላል፡፡ ከአሜሪካ የመጣው ዳያስፖራ እንደ አውራ ዶሮ ሊከመርባት ነው ብለን ስንሰጋ፣ ያላሰብነው ነገር ከተፍ ይላል። ብቻ ዘመኑና ትውልዱ ወዴት እየሄደ እንደሆነ ስናስብ ያስደነግጣል፣ እየሳቁ መደንገጥ!
ኢትዮጵያዊያን በአንድ በኩል “በቅኝ ያልተገዛን፣ የሥነልቡና ቀውስ ውስጥ ያልገባን፤ ክብራችንን ያላስነካን” እያልን፣በሌላ በኩል እግራቸው ሥር የወደቅን ባሮች መሆናችንን እናያለን፡፡ “ሀገራችን ቅድስት ናት” እያልን ራሳችንን ስንሸነግል፣ በወሲብ ጥማት የተቅበዘበዝን እንደሆንን ገበያውን ያጥለቀለቁት የወሲብ መጽሐፍት ብዛት ይመሰክሩብናል፡፡ በአጭሩ ቴአትሩ ያፈጠጠውን እውነት ነው በጥበብ ከሽኖ የሚያቀርብልን፡፡ “ወደ ራሳችን እንመልከት፣ያለነው ቅድስናና ክብር ውስጥ ሳይሆን ውርደትና ቅሌት ውስጥ ነው፤ ታሪካችንን፣ ክብራችንንና ሞራላችንን ሸጠናል” ይለናል፡፡ የማንከራከርበት ሃቅ ነው፡፡  
ትንሽ ቅር ያለኝ ቴአትሩ በአንድ ፆታ ላይ ብቻ ማነጣጠሩ ነው፡፡ ባል ፈላጊ ሴቶች ብቻ መቀረፃቸው  እውነታውን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በዕድሜ የገፉ ሴቶችን ፎቶግራፍ እያገላበጡ፣ አሜሪካ ለመሄድ ክንፍ የዘረጉ ወንዶችም ሞልተዋል። በእርግጥ ባል ፈላጊ ሴቶች እንደሚበዙ አሌ አይባልም!
እንደኔ እንደኔ ቴአትሮቻችን የሌለ ሕልምና ቅዠት እያመጡ፣ በምድር ላይ የማይደረግ ታማኝነት እየከመሩ፣  የመንግስተ ሰማያትን ሕይወት ሊያሳዩን ከሚሞክሩ፣ እየነደድንባት ያለችውን የዚህን ዘመንዋን ሲኦል አራቁተው በማሳየት፣ የምንወጣበትን መንገድ እንድንፈልግ ቢያነቃቁን ይመረጣል፡፡ ለኔ የዘካርያስ ብርሃኑ “የበዓል እንግዶች” ያንን ሚና ተጫውቷል፡፡ ዘመናችንን እንድንዋጅ የሚረዳን ቴአትር ነው፡፡  

Published in ጥበብ
Page 7 of 13