ጥንት ዱሮ አያ ቋቴ የሚባሉ ብልህ ሰው ነበሩ ይባላል፡፡ የአያ ቋቴ መታወቂያ ሰው እህል ለመዝራት ገና መሬቱን ሳያለሰልስ እሳቸው እርሻ መጀመራቸው ነው፡፡
“አያ ቋቴ?” ይላቸዋል አንዱ፡፡
“አቤት” ይላሉ
“ምነው እንዲህ ተጣደፉ? በጊዜ እርሻ ጀመሩ?”
“በጊዜ ቋቴን (የዱቄት እቃዬን) ልሞላ ነዋ” ይላሉ፡፡
“መሬቱ የት ይሄድቦታል? ቀስ ብለው አያርሱትም ታዲያ?”
“አርሼውስ የት ይሄድብኛል? ብዘራበትስ መች እምቢ ይላል?”
አያ ቋቴ በጊዜ በማለዳ እየተጣደፉ ሄደው አዝመራቸውን ሲሰበስቡ፤ ገና ያልዘሩ ሰዎች፤
    “አያ ቋቴ?”
    “አቤት”
“አሁን አዝመራው የት ይሄድብዎታል? እንዲህ ሰማይ ዐይኑን ሳይገልጥ እየሮጡ የሚሄዱት?”
“ፈጥኖ የደረሰ እህል አንድም ለወፍ አንድም ለወናፍ ነው፡፡ በጊዜ እጅ የገባ ነገር ጥሩ ነው፡፡ ቋቴ በጊዜ ሞልቶ ቢገኝ ምን ይጎዳኛል?” ይላሉ፡፡  
ቆይተው እየተጣደፉ ሊያስፈጩ እህል በአህያ ጭነው ሲሄዱ ሰዎች ያገኙዋቸዋል፡፡
    “አያ ቋቴ?”
    “አቤት”
    “ወዴት ነው እንዲህ እየተጣደፉ የሚሄዱት?”
    “ወደ ወፍጮ ቤት”
    “እንዲህ በጠዋት፣ እንዲህ እየሮጡ?”
    “አዎን እንዲህ በጠዋት፣ እንዲህ እየሮጥሁ”
    “ምነው ጦር መጣ እንዴ? ፀሐይ ሞቅ ሲል ቀስ ብለው አይሄዱም?”
    “ለቋቴ፡፡ ቋቴ በጊዜ እንዲሞላ ነዋ!”
አያ ቋቴ እህላቸውን አስፈጭተው ማጠራቀሚያ ቋታቸው ውስጥ ከትተው እያስጋገሩ ሲበሉ፣ ሰዉ ገና እርሻ ላይ ወዲያ ወዲህ ይላል፤ በማህል አንዱ ይመጣና
    “አያ ቋቴ?”
    “አቤት”
    “የምንበላው አጣን እባክዎ ዱ    ቄት ያበድሩን”
ሌላው አዛውንት ይመጡና፤
    “የእገሌ ቤተሰብ በረሀብ ሊያልቅ ነው እባክዎ ትንሽ ዱቄት ካለዎት?”
ቀጥሎ የእድሩ ዳኛ ይመጡና፤
“አያ ቋቴ”
    “አቤት”
“እባክዎ የእገሌ ልጅ ሞቶ ለቀስተኛውን እምናበላው አጣን፤ እንደሚያውቁት እህል አልደረሰልንም?”
አያ ቋቴም አይ ያገሬ ሰዎች፤ “ለልመና ሲሆን ሰው ሳይቀድማችሁ ትነሳላችሁ፡፡ እኔ ለቋቴ ማለዳ ስነሳ ታሾፋላችሁ! መቼ ነው ጊዜ ቋት መሆኑ የሚገባችሁ?” አሉ ይባላል፡፡
    *     *     *
ከአያ ቋቴ የምንማረው ለዓላማችን ስንል በጠዋት መነሳትን ነው፡፡ አስቀድሞ መዘጋጀትን ነው፡፡ በጊዜ መሰነቅን ነው፡፡ በጊዜ መክተትን ነው፡፡ ጊዜ የትግል ቋት ነው፡፡ “ጊዜ የስልጣን እጅ ነው” ይላሉ አበው፡፡ ሰው ሳይቀድመን ለልመና ከመነሳት ይሰውረን፡፡
ገጣሚው ራልፍ ኤመርሰን “አልኮል፣ ሐሺሽ፣ ፕሩሲክ አሲድ፣ ካናየን ደካማ ሱሶች ናቸው፡፡ ዋና መርዘኛ ዕፅ ጊዜ ነው” ይለናል፡፡
“የሰዓቱ እጀታ ከምናስበው በላይ እየተንቀረፈፈ ነው፡፡ ረፍዶብናል!” የሚሉት መዝሙር አላቸው ቦሄማውያን፡፡ መርፈዱን መገንዘቢያችን ደቂቃ ወይም ሰከንድ ላይ ነን፡፡ በወሬ የምንፈታው ጦር የለም። በወሬ የምንፈታው ዳገት የለም፡፡ ሁሉ ነገር ሥራ ይፈልጋል፡፡ ነገን ዛሬ እንሻማው፡፡ “ዛሬ ላይ ሆነን ከነገ መስረቅ ነው (Plagiarizing the future)” እንደተባለው ነው፡፡
ዛሬ፤ የለመድነውን ይዘን ከመቀጠል ሌላ የአስተሳሰብ ለውጥ ሽታው ጠፍቷል፡፡ ዕውቅናና ገንዘብ የማሰባሰቢያውን ማሺን እጁ ያስገባ ሰው የሚነግስበት ዘመን ሆኗል! ይሄንን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ብለን እየተጓዝን ነው፡፡ ሆኖም ፓርቲ እየዘቀጠ ሲሄድ ባለፀጋ መሆን (Fattening) ይበረክታል፡፡ ዝነኛ መሆን ግብ ይሆናል፡፡ ቲፎዞ በመሰብሰብ የሚመራ መሪ ባዶ ገረወይና ነው፤ እንደሚባለው ዓይነት ነገር ይዘወተራል፡፡ ይለመዳል፡፡ ዲሞክራሲ ይህ ከሆነ ዲሞክራሲ ራሱ ገና ዲሞክራሲያዊ መሆን ያስፈልገዋል። (Let’s Democratize Democracy-Fareed Zekaria)
ለማስመሰል በማይሆን ተስፋ መፅናናት ብዙዎቻችንን ላልተጨበጠ መንገድ ይዳርገናል፡፡ አስተሳሰባችን አሜሪካዊው ድራማቲስት ብሩክ አትኪንሰን “አንድ ቀን በፀሐይ ዙሪያ” በሚለው ፅሑፍ ተስፈኝነትን ሲገልፅ፤ ካለው ጋር የሚሄድ ነው፡፡ “አንዳች ተዓምራዊ-ሚሥጥራዊ መንገድ ፍቅር ሁሉንም ድል ይመታል፣ መልካሙ ነገር መጥፎውን በሁለንተናዊው ዓለም ሚዛን መሰረት ይረታል፤ እናም በ11ኛው ሰዓት ክፉ ነገር በእኛ ላይ ከመምጣቱ በፊት አንዳች ገናናና ታላቅ ኃይል ያቆመዋል፤ ይከለክልልናል!” ከዚህ ቢሰውረንና ለመስራት ብንነሳ፣ ለመደራጀት ብንዘጋጅ፣ ውጣ ውረዳችንን ከወዲሁ በተጨባጭ ልንበግረው ብንጣጣር ይሻላል፡፡ ልባችን ዘውድ ለመጫን ያስብ እንጂ እጃችን አፈር አልጨበጠም፡፡
የተለመደ መፈክር፣ የተለመደ የአፍ ወረርሺኝ፣ የተለመደ ከላይ ወደታች ትዕዛዝ፣ የተለመደ ዝቅጠት፣ የተለመደ በሙስና ወደ ሀብት ጉዞ፤ ተፈጥሮ የሰጠን ይመስል ተቀብለነው የምንኖር ልማድ ሆኗል። መብራት ሲጠፋ ለመድነው፡፡ ውሃ ሲጠፋ ለመድን፡፡ ስልክ መስመር ሲጠፋ ለመድን፡፡ ኑሮ ሲከፋ ለመድን፡፡ ይሄንኑ ማማረርንም ለመድን… በመልመድ ተሞላን፡፡
ዛሬ በአገራችን ኢ-ሜይል ሳይሆን “ስኔይል” ተሽሏል እየተባለ ነው፡፡ ከኢሜይል ይልቅ የቀንድ-አውጣ ጉዞ ይሻላል እንደ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር እየተንቀረፈፍን ነው፡፡ የቴሌ ሥርዓት ዋናው አንቀርፋፊያችን ነው እተባለ ነው፡፡ በእንሰቅርት ላይ ጆሮ ደግፋችን መዓት ነው!
Death and taxes and childbirth! There’s never any convenient time for any of them!
የ “ነገም ሌላ ቀን ነው” ደራሲ ማርጋሬት ሚሼል “ሞት፣ ቀረጥ እና ልጅ-መውለድ ምኔም ምቹ ጊዜ ኖሮት አያውቅም” ትላለች፡፡ ምጡ ከደረሰ ማሰቃየቱ አይቀርም ነው፡፡ ሦስቱ አንድ ላይ ሲመጣማ የመርገምት ሁሉ መርገምት ነው፡፡
በ11ኛው ሰዓት ይላሉ ፈረንጆች፡፡ አዬ፤ አማርኛ ቢያውቁ “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ይሉ ነበረ። ይሄንን ክፉኛ ለምደናል፡፡ ዕዳ የምንከፍለው በ11ኛው ሰዓት ነው፡፡ ስልክ የምንከፍለው በ11ኛው ሰዓት ነው። (ስልክ ባይኖርም)!! መብራት የምንከፍለው በ11ኛው ሰዓት (ውሃው ባይኖርም)!! ለፈተና የምናጠናው በ11ኛው ሰዓት (ትምህርት ቢደክምም ባይደክምም)!! ወደ ሐኪም የምንሄደው በ11ኛው ሰዓት!! (ቢጭበረበርም ባይጭበረበርም)!! ይሄን ልማድ ካልተውን መቼም ህይወትን አንረታም፤ ባላንጣችንንም ተፎካካሪያችንንም አናሸንፍም!!
ሼክስፒር በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር፤
“ዛሬ ለወግ ያደረግሺው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል”፡፡ የሚለን ለዚህ ነው፡፡”    

Published in ርዕሰ አንቀፅ

                     “ሳንቲሞችን ጠብቃቸው እንጂ ብሮች ያለምንም ችግር እራሳቸውን ይጠብቃሉ” የሚለው አነጋገር ለተነሳሁበት ጉዳይ የልብ ራስ ሆኖ የሚቆጠር ነው። ሳንቲሞችን ከብክነት መከላከል ንፉግነት ወይም ስግብግብነት አለመሆኑም ሰሚ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ባለፈው ታህሳስ ወር ሁለተኛ ሳምንት መግቢያ ላይ ወደ አዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ብቅ ብዬ ነበር፡፡ ምክንያቴ ደግሞ በታክሲ ከቦታ ወደ ቦታ ስንቀሳቀስ ከታሪፍ በላይ እንድከፍል መደረጌን ለማስቆምና ሳንቲሞችን ለመቆጠብ ነው። መንግሥት በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ይፋ ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ የታክሲ ታሪፍ፣ አሁንም ድረስ በሥራ ላይ ነው፡፡ ምናልባትም በየካቲት ወርም ሊቀጥል ይችላል፡፡ በታሪፉ መሠረት፣ እስከ 2.5 ኪሎ ሜትር 1.45፣ እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር 2.80፣ እስከ አስር ኪሎ ሜትር 4.00 ብር ነው ክፍያው፡፡ እኔ በብዛት የምገለገለው የመጀመርያ ሁለቱን ርቀቶች ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር የነበረው ታሪፍ 2.65 ቢሆንም፣ ታክሲዎች በራሳቸው ጊዜ ጨምረው ሕዝቡን 2.70 (ሁለት ብር ከሰባ ሳንቲም) ሲያስከፍሉት መክረማቸውን የትራንስፖርት ቢሮው የመረጃ ማዕከል ባልደረባ ገልፃልኛለች። በታህሳስ ወር የተደረገው የታሪፍ ጭማሪ እነሱ በጉልበት በጨመሩት ላይ ተጨምሮ 2.80 ሆነ ማለት ነው፡፡

ሕጉን የሚያስከብርና ለሕዝብ ጥቅም የሚቆም አካል አለመኖሩን በሚገባ የሚያውቁትና የትራንስፖርት ቢሮውን ልብ በትክክል የተረዱት የታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶች አሁንም በራሳቸው ጊዜ ዋጋ ጨመሩ። 1.45 የነበረውን ወደ 1.50፣ 2.80 የነበረውን 2.90 አሻገሩት፡፡ በዚሁ በጥር ወር ደግሞ 2.80 ሊከፈልበት የሚገባው ጉዞ 3.00 ብር እየተከፈለበት ነው፡፡ የታክሲ ረዳቶች ሶስት ብር ሲጠይቁ ትንሽም እንኳ ጥፋት እየፈፀሙ መሆናቸው አይሰማቸውም። በእነሱ ዘንድ ትክክለኛ ሥራ እየሰሩ ነው፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ጥር 21 ቀን 2006 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሄጄ ነበር፡፡ መገናኛ የየካና የቦሌ ክፍለ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ጽ/ቤቶች አሉ፡፡ “ሕግ የሚያስከብርልኝ ማነው?” አልኳቸው፡፡ የየካው ትራንስፖርት ቢሮው ባልደረባ “ማንም!” የሚል ቁርጥ ያለ መልስ አልሰጡኝም፡፡ የነገሩኝ ቀኑን፣ ሰዓቱንና የመኪናውን የሰሌዳ ቁጥር ይዤ ለሚመለከተው የክፍለ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ማመልከቻ በመፃፍ ክስ ከመሰረትኩ፣ እኔ በተገኘሁበት ተከሳሹ ቀርቦ እንደሚጠየቅና እንደሚቀጣ ነው፡፡ እሳቸው በዚህ መንገድ አንድ ሹፌር ማስቀጣታቸውንም ገለፁልኝ፡፡

በየጊዜው በማድረጋቸው ጉዞዎች በቋሚነት የሚገጥሙኝ ችግሮች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በየካ ትራንስፖርት ቢሮ ባልደረባ ምክር መሠረት ማመልከቻ አያያዝኩ የምቆምባቸውን የትራንስፖርት ቢሮዎች ሳስበው አቶ መለስ ዜናዊ እንዳሉት “ሳስበው ሳስበው ደከመኝ” በጣም ደከመኝ፡፡ ይህ ደግሞ በግልጽ የሚያሳየው ታሪፉን የሚያስከብር ወይም ለማስከበር የተነሳ አንድም አካል አለመኖሩን ነው። ሰውየው ከእንደበታቸው አይውጣ እንጂ ያሉት “ማንም ህግ የሚያስከብር የለም!” ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከስምንት ሺህ በላይ ባለ ቀይ ሰሌዳ ታክሲዎች አሉ፡፡ ከእነሱ ሌላ ከሁለት ሺህ የማያንሱ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሚኒባሶች አሉ፡፡ አንድ መኪና ከአስር ያላነሰ የደርሶ መልስ ጉዞ (70 ኪሎ ሜትር) በየቀኑ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጉዞው በትርፍ የሚይዛቸውን ጨምሮ በአማካይ ለ150 ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይታመናል፡፡ እነዚህ ታክሲዎች በየቀኑ ከታሪፍ በላይ 150ሺ ብር ክፍያ ይሰበስባሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በወር 4.5 ሚሊዮን፣ በዓመት 54 ሚሊዮን ብር ማለት ነው፡፡

እያንዳንዱ ተሳፋሪ እየከሰሰ መብቱን እንዲያስከብር ክፍት መተው ሕገወጥ ድርጊት እንዲፈፀም ልቅ ከመተው የሚተናነስ አይደለም፡፡ ለእኔ ይሄ መንግሥት ህግን ማስከበር እንዳቃተው ማሳያ ነው፡፡ ታክሲ ላይ ብቻ አይደለም፣ በየትኛውም የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ለሸማቹ ወይም ለተገልጋዩ የሚያስብ አእምሮ አልተፈጠረባቸውም የሚያሰኙ ናቸው፡፡ በሸማቹ ወይም በተገልጋዩ ሕዝብ ኪስ የሚያድር ገንዘብ ነገ ተመልሶ የእነሱ መሆኑን ማሰብም ተስኗቸዋል፡፡ ኪሱን ገልብጠው አራግፈው ወደ ቤቱ ቢመልሱት የሚሰማቸውን ደስታም መገመት አይከብድም፡፡ ሕዝቡ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው ከታክሲ ረዳቶች ጋር ተጨቃጭቆ መብቱን ማስከበር ይችላል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ጉዞዬ በማቀርበው ጥያቄ የገጠመኝ ዘለፋና ማሸማቀቅ ሌላ ተጨማሪ ክፍያ ከፍሎ መገላገል የሚያስመኝ ነው።

በእኔ እምነት ታሪፉንም ሆነ ሌሎች የተገልጋዩን ሕዝብ ጥቅሞች ማስጠበቅ ያለባቸው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የእኔ አይነት ተሳፋሪዎች ሳይሆኑ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት፣ የየክፍለ ከተማው ትራንስፖርት ቢሮዎችና የባለ ታክሲዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ የተቋቋሙት የታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት ናቸው፡፡ በተለይ የታክሲ ማህበራት “ጥቅማችን ለምን ይቀርብናል” ብለው እስካልተነሱ ድረስ የቀጠሯቸውን የታክሲ ረዳቶችና ሹፌሮች “እጃችሁን ወደ ደንበኞቻችን ኪስ አትክተቱ” ማለት ይችላሉ፡፡ በትክክል በጉዳዩ ከአመኑበት ደግሞ ቃላቸው ተግባራዊ መሆኑን እንደኛው ተሳፋሪ እየሆኑ ሊፈትሹት ሊከታተሉት ይችላሉ፡፡ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ከልብ ከተነሳ ችግሩን መፍታት ያቅተዋል ብዬ አላምንም፡፡ የመጀመርያ እርምጃ መሆን ያለበት የታክሲ ባለንብረቶችን፣ ሹፌሮችንና ረዳቶቻቸውን የተሳፋሪውን ጥቅም የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው ማስገንዘብ ማሳመን ነው፡፡ ሁለተኛው እያንዳንዱ ታክሲ እንደሚሄድበት መስመር ሁሉ በግልጽ በሚታይ ቦታ የታሪፉን ዝርዝር እንዲለጥፍ ማድረግ፣ ማስገደድና መቆጣጠር ነው፡፡

ሶስተኛው ማህበራት የሚደራጁት የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ግዴታንም ለመወጣት በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ማህበር አባሉ ሕግ ማክበሩን እንዲከታተል የሚያደርግ ሕግ ወይም ደንብ ማውጣት ነው። በመጨረሻ ከሳንቲም መልስ ችግር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ጉዳቶችንና ውዝግቦችን ለማስቀረት የሚታየኝ አማራጭ መፍትሄ፣ ባለታክሲውና ተሳፋሪው በየተራ እየተጉዱ መልስ የማይጠየቅበት ዝግ ማለትም ብር ፣ ሁለት ብር፣ ሶስት ብር ወዘተ--- የሚሉ ታሪፎች ማውጣት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በተለያየ ጊዜ ከታሪፍ በላይ አስከፍለውኝ ለሚመለከተው አካል አቤት ለማለት ብዬ የሰበሰብኳቸውን የታክሲ ሰሌዳ ቁጥሮች ቀድጄ የጣልኳቸው ሲሆን “መልስ አለኝ” ብዬ ከመናገርና የሚሰጡኝን ከመቀበል ውጪ መከራከሩንም አቁሜዋለሁ፡፡ እኔ የምናፍቀው ሕግ የሚያስከብር መንግሥት ማየት ብቻ ነው፡፡ ያኔ ዘረፋ ይቆማል፡፡

Published in ህብረተሰብ
Monday, 10 February 2014 07:08

የውሸት ደዌ በምን ይድናል?

ውሸት በቀላሉ ሲተረጐም ከእውነት ጋር የሚቃረን፤ ያልሆነውን ሆነ፣ ያልታየውን ታየ፣ ያልተሰማውን ተደመጠ ብሎ ማውራት ወይም ማስወራት ነው ብሎ መግለጽ ይቻላል፡፡ ውሸት በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በማህበራዊ ግንኙነቶች፣ በእምነት ቦታዎች፣ በጤና ተቋማት፣ በግለሰቦች፣ ወዘተ የሚስተዋል ጣጣ ነው፤ አንዳንዴ እንዲያውም በዋሾ ሰዎች ጦስ የሞቀ ትዳር ሊፈርስ፣ የንጹሃን ደም በከንቱ ሊፈስስ ይችላል፡፡
አንዳንድ ሰዎች እንዲያውም በውሸት በሽታ ከመለከፋቸው የተነሳ ራሳቸውን ጭምር ሲዋሹ ይስተዋላሉ፤ ለምሳሌ እናቱ በየቤቶቱ እየዞረች እንጀራ በመጋገር፣ ልብስ በማጠብ፣ ወይም ቤት በመጥረግ ያሳደገችው ምስኪን፤ “እናቴ ነፍሳቸውን ይማረውና ሞልቶ የተረፋቸው ሃብታም ነበሩ፤ ምን ዋጋ አለው፤ ደርግ ያንን ሁሉ ሐብት ወርሶ ሜዳ ላይ ጣላቸው፤ በዚሁ ምክንያት ቀሪ ዘመናቸውን በብስጭት አሳልፈው በደም ግፊት ሞቱ፡፡” ብሎ ይዋሸናል፡፡ አድማጮችም የተናገረው እውነት ቢመስለን አይፈረድብንም፤ እንባው እየተናነቀው ነዋ የሚያወራን፡፡
ችግሩ ግን ምን አልባት የዋሾውን ሥረ- መሠረት የሚያውቅ ሰው ከአድማጮች መሃል የተገኘ እንደሆነ ነው፤ እሱም ቢሆን ሊፈጠር የሚችለው ትዝብት ብቻ ሊሆን ወይም “ለምን ትዋሻለህ? እናትህን እኮ አውቃለታለሁ” ብሎ ዋሾውን የሚጠይቅ ካለም “ተመሳስላብህ እንጂ እንኳን እናቴን እኔንም አታውቀኝም” የማይልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የተጠናወተው የውሸት በሽታ ጓደኛውን ሳይሆን ራሱን እንኳ እንዲዋሽ ያስገድደዋልና፡፡
ያጣ የነጣ ኪስ ይዞ በምሳ ሰዓት መንገድ ለመንገድ ሲንከራተት ቆይቶ፤ ወደ ሥራ ቦታው ሲመለስ “አቤት ምሣ! እንዲህ ያለ ሥጋ በህይወቴ በልቼ አላውቅም!” እያለ ራሱን የሚዋሽ ከንቱም ያጋጥማል፡፡ ይህን ሁሉ የሚለፈልፈው ደግሞ ተጠይቆ አይደለም፤ በውስጡ ያለውን የበታችነት ስሜት በውሸት ያካካሰው እየመሰለው ነው፡፡ የውሸት በሽታ ለከት የለውማ! የደፈረሰ ውሃ በሰፈሩ ከጠፋ ሳምንትና ከዚያ በላይ የሆነው ዋሾም “ገላዬን የምታጠበው በጠጅ ነው” ብሎ ለማውራት አይገደውም፡፡ ምክንያቱም የተጠናወተው የውሸት በሽታ ነው፡፡
“እኔ አባታችሁ ምቀኛ በዝቶብኝ፣ አለቃዬ ጠምዶ ይዞኝ፣ የእንትን ብሔር አባል በመሆኔ ወደ ታች እየቀበሩኝ እንጂ እውቀቴኮ ከማንም በላይ ነበር፤ ምን ዋጋ አለው? ደሞዜ ለዘመናት እንደ ካሮት ቁልቁል ሲወርድ የሚኖረው፣ እናንተንም በአግባቡ የማላሳድጋችሁ ለዚህ ነው” የሚለው የውሸት አቁማዳም ብዙ ነው፤ በብሔር ምክንያት ጭቆና የሚደርስበት የለም ብሎ መከራከር ባይቻልም ለግለሰቡ ድህነት ሰበቡ ግን ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድም በደሞዙ ይጠጣበታል፤ ወይም ደባል ሱሱን ያስታግስበታል፡፡
“ማጨስ ለሳንባም ሆነ ለአጠቃላይ ጤና ጠንቅ ስለሆነ ከዚህ ድርጊት መታቀብ አለባችሁ” ብሎ ከአንድ ሆስፒታል ግቢ ይመክር የነበረ አንድ የጤና ባለሙያ፤ እዚያው አደባባይ ሳለ መሀረብ ሲያወጣ ሁለት ሲጋራዎች ከኪሱ ድንገት ወድቀውበት ምን ያህል እንደተሳቀቀ አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ያሳፈረውና እኛንም (በቦታው የነበርነውን ታዳሚዎች) ያስገረመን ግን ድርጊቱን ለማስተባበል የፈጠረው ከንቱ መወላፈት ነው፤ “ይቅርታ ከእግሬ ስር ሲጋራ የጣላችሁ ሰዎች አንሱና ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ውስጥ ጨምሩት” ሲል ሳቃችንን መቆጣጠር አቅቶን መበተናችን መቸም አይረሳኝም፡፡
በየመዝናኛ ቦታዎች፣ በሥራ ተቋማትና በመሳሰሉት አጋጣሚዎች ከሚያገኛቸው ሴቶች ጋር ሲቀብጥ እየዋለ፣ እያመሸና እያደረ ከሰው ፊት “ባለቤቴኮ ሁለመናዬ ናት፤ እናቴ፣ ትዳሬ፣ ህይወቴ ማለት እሷው ናት፤ እሷ ባትኖር ኖሮ ህይወቴ ምን ያህል ለአደጋ የተጋለጠ ይሆን እንደነበር እግዜር ነው የሚያውቀው” የሚል የውሸት አጋሰስም እጅግ ብዙ ነው፡፡ ከሰው ፊት ሲሆን ስለሚስቱ መቀባጠር ይቀናዋል፤ ዘወር ስትል ግን ምላሱን ያወጣባታል፡፡ ከሰው ፊት ያወደሳት እውነት ስለሚመስላትም የውሸት አቁማዳውን ለመሙላት ምቹ ሁኔታ ይፈጠርለታል፤ የትም የሚልከሰከሰው “ትዳሩን ለማቃናት፣ የሚስቱን ህይወት ለማሻሻል ደፋ ቀና እያለ…” ይመስላታል፡፡
ተንቀሳቃሽ ስልክ ከመጣ በኋላማ  የውሸታሞች ቁጥር በአያሌው ተበራክቷል፡፡ መገናኛ ሆኖ “ቃሊቲ ነኝ” የሚል፤ ከውሽማው ጋር አልቤርጐ ውስጥ እየቀበጠ፣ ድንገት ሚስቱ ስትደውል “ሥራ ቦታ ነኝ፣ ስብሰባ ነኝ፣ ወዘተ…” የሚለውን ቀልማዳ ቤቱ ይቁጠረው፡፡
ከሁሉ የሚገርመኝ ግን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የእምነት ሰዎች ውሸት ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ የሃይማኖት ሰዎች ብዙ ተከታዮች አሏቸው፤ ያሉትን ነገር ሁሉ የፈጣሪ ቃል አድርገው የሚያምኑ ብዙ የኔቢጤዎች አሉ፡፡ ኑሮ ከመርግ በላይ ከብዶን መከራችንን እያሳየን እያለ የመንግሥታችን መሪዎች ሞቅ ባላቸው ቀን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ይሉና “የኢኮኖሚ ግሽበቱን በ20 በመቶ ቀንሰነዋል፤ ዕድገታችንም ባለ ሁለት አኃዝ ደረጃውን እንደጠበቀ በፍጥነት ወደፊት እየገሰገሰ ነው” ሲሉ ያጃጅሉናል፤ ውሸት መሆኑ የሚታወቀው ግን ዓለም አቀፍ ገለልተኛ ድርጅቶች  የዕድገታችንን ልኩን ሲነግሩን ነው፡፡
ሌላው ባለስልጣንም “የሕግ የበላይነት ሰፍኗል፤ የመጻፍ፣ የመናገር፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና የእምነት ነፃነት ተከብሯል” ሲል በሬዲዮና ቴሌቪዥን መግለጫ  ይነግረናል፡፡ አባባሉ ምን ያህል ከእውነት ጋር እንደሚጋጭ የምናውቀው ግን እኛው የፈረደብን ዜጐች ነን “ኧረ እባክህ እየዋሸኸን ነው፤ እዚህ ቦታ ያለ ፍርድ የታሰሩ፣ በፀጥታ ኃይል አባላት የተደበደቡ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ዜጐች አሉ” ሲባልም የሚሰጠው መልስ “ይሄ የፀረ - ልማት ኃይሎች ወሬ ነው” ይለናል፡፡
መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ “ዜጐቼን የሚገርፉ፣ የሚዘርፉ፣ የሚገድሉና የሚያንገላቱ ባለሥልጣናት ወዮላቸው” የሚል ጨዋ መሳይ አስተያየት የሚያሰማው በምርጫ ዋዜማ ላይ ነው፤ ከምርጫ በኋላ ለህዝብ ታዛዥ መስሎ የመቅረቡና የውሸት ትህትናው ሁሉ እንደ ጉም በንኖ ይጠፋና “ማን አባቱ ተናግሮኝ” የሚል ጉልቤነቱን ይቀጥልበታል፡፡ የመንግሥት ባለስልጣናትን ውሸት ለመቀነስ ሲባል ምን አለበት “ምርጫ” በየሶስት ወሩ ቢኖር!
አንዳንድ የእምነት ቦታዎች አካባቢ የሚስተዋለው የውሸት ናዳም በእጅጉ ይገርመኛል፤ አንድ ሰባኪ በየአገኘው አጋጣሚ “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለሌላው ይስጥ፤ ገንዘቤ የኔ ብቻ ነው አትበል” እያለ ሲያስተምር ሚስቱ ሁልጊዜ ታዳምጥ ነበርና ራሷን መጠየቅ ትጀምራለች “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለሌለው መስጠት አለበት የሚለው የአምላክ ቃል ነው?” ስትልም ባሏን ጠይቃ ታረጋግጣለች፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሰባኪው ባሏ ስብከት ነበረበትና ልብስ መቀየር ፈለገ፤ ግን የፈለገውን ልብስ አጣ፡፡ ባለቤቱን ሲጠይቃት “ትምህርትህን ሰምቼ፤ የጌታ ቃል መሆኑን ተረድቼ ምንም ለሌለው ድሃ ሰጠሁት” አለችው፡፡ ባሏ ምን አለ መሰላችሁ? “እኔ ሌሎች እንዲሰጡ ነው እንጂ የእኔን ስጭ አልኩሽ?” ብሎ አናቷን አላትና ሞተች ይባላል፡፡
ይሄን ትልቅ  ጣጣ ያመጣውም ውሸት ነው፤ ውሸቱ ከመጽሐፉ አይደለም፡፡ ሰባኪው የተጠቀመበት መንገድ እንጂ “የምእመናን ሃብት ሲሆን ለድሃ ይሰጥ፤ ሰባክያን ግን ሃብት ያጋብሱ” የሚል አስተምህሮ የለማ፡፡ የሃይማኖት መጻሕፍት ሁሉ፣ የሚደነግጉት ሃይማኖታዊ ሕግ ሁሉ ለአማንያኑ በጠቅላላ እንጂ ለምእመናን ብቻ አለመሆኑ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ አለዚያ እንደ ዓለማዊው ሕግ ሆነ ማለት ነው፣ የፈለጉትን ወንጀል ሰርተው “ያለ መከሰስ መብት አለን” እንደሚሉት ዘመነኞች፡፡
እዚህ ላይ ከአስር ዓመት በፊት በነበርሁበት አካባቢ የተከሰተ አንድ አጋጣሚ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አንዲት ክርስቲያን እና አንድ ሙስሊም ተጋብተው ይኖሩ ነበር፤ ልጆች ወልደው ሃብት አፍርተው በፍቅር ሲኖሩ ድንገት አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ተከሰተ፡፡ የሙስሊሙ  ሚስት ክርስቲያኗ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡ መሞቷ አይደለም ችግሩ፤ ይልቁንም “የት ትቀበር?” የሚለው ጉዳይ ነበር በርካታ ሰዎችን ያነጋገረው። ድሮውንም የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮችን ጋብቻ ይቃወሙ ለነበሩ ወግ አጥባቂዎች፣ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸውም በመቃብር ምክንያት ነው። ሁለቱም ወገኖች የመቃብር “ዕድል” ነፈጓትና ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊም ከማይቀበሩበት ሜዳ ላይ ተቀበረች፡፡
የቀብሯ ሥርዓት ከተፈፀመ  ከተወሰኑ ቀናት በኋላ አንድ አስገራሚ ነገር ከተማዋን ያምሳት ጀመር፤ እሱም “ዕገሊት ስትጮህ ተሰማች፤ በዚህ ቀንም እንደምትነሳ ተናገረች” የሚል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የከተማዋ ነዋሪ ሥራውን እየፈታ ወደ ሟቿ መቃብር መጉረፉን ተያያዘው፤ ይህን የሰማው ፖሊስም ህዝቡን ለመግታት ሲሞክር የባሰ ችግር ተፈጠረ፡፡ የነበረው አማራጭ “ሄጄ አያለሁ፤ አትሄድም፣ የተፈጠረ አዲስ ነገርም የለም” ከማለት ይልቅ አይቶ እንደሚያምን በነፃነት መተው ሆኖ ተገኘ፡፡
በተለይ “በአርባኛው ቀኗ እንደምትነሳ ነግራናለች” የሚሉ ሰዎች ጉዳይ ትልቅ ትኩረት አግኝቶ ነበርና በሞተች በአርባኛው ቀን ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የከተማዋ መንገዶች እጅግ በሚያስደንቅ መልኩ ተጨናነቁ፤ እንኳን ፖሊስ ሌላ ኃይል ቢመጣም የሰውን ማዕበል ሊገታው የሚችል አልነበረም፤ እኔም ከታዳሚው አንዱ ስለነበርሁ በዚያ የህዝብ ማዕበል እየተገፋሁ ከአንድ ሰዓት የትርምስ፣ የግፊያና ወከባ ጉዞ በኋላ ከቦታው ደረስሁ፤ ግን ያን ያህል ከተማዋን እንደ ገብስ ያመሳት ወሬ ውሸት ነበር፡፡
በነበረው ትርምስም የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፡፡ በዚህ የተነሳ እኔ ብቻ ሳልሆን በቦታው የነበረው ህዝብ ሁሉ መጀመሪያ “ስትጮህ ሰማኋት” ያለውን ሰው በቦታው ቢያገኘው፣ እርግጠኛ ነኝ የዘለዓለም ቤቱን ከሟቿ መቃብር ጋር ያደርገው ነበር፡፡
የውሸት ደዌ በጠበል፣ በህክምና፣ በአባይ ጠንቋይ፤ ወይም በቃልቻ የሚድን አይደለም፡፡ በማህበረሰቡ ንቃት፣ ድፍረትና ውሸታሙን “እረፍ፣ ከዚህ ድርጊትህ ታረም!” ባይነት እንጂ፡፡ የውሸት ደዌ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከማህበረሰባች ውስጥ እንዲጠፋ ከፈለግን ለእውነት ዋጋ መስጠት መጀመር አለብን፡፡

Published in ባህል

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ተቀምጠን እየሰቀልን እኮ ቆመን ማውረድ አቃተንሳ! ልክ ነዋ…ይኸው በምኑም፣ በምናምኑም በአጋጣሚም ቢሆን ‘ወደ ላይ’ ያወጣናቸው “አይ፣ በቃችሁ…” ምናምን ስንል የሚሰማን አጣን፡፡
እኔ የምለው… መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… “የተሸነፍነው ስፖርት ጋዜጠኞቹ ግራ አጋብተውን ነው…” ምናምን ተባለ የተባለው…በቃ እንደዚህ የ‘ቻርሊ ቻፕሊን ወራሾች’ ምናምን ሆነን እንቅር! ጭራሽ ታክቲክና ስትራቴጂ በጋዜጠኞች ሆነና አረፈው!
ችግሩ ምን መሰላችሁ…በዛ መያዣ መጨበጫ ባጣን ሰሞን ጋዜጠኞች የኳስ ሰዎቻችንን አወጣን አወጣንና እላይ ‘ጉብ’ ማድረግ! ነገሩ ሲረጋጋና ጎል እያቃሙንና ውራ እያደረጉን ሲልኩን “ለነገሩ እኮ ብዙ ይቀራችኋል…” ሲባል ማን ይስማ! እናላችሁ… እንዲሁ “ከዚህ ያክል ቡድኖች መካከል ምርጥ ተባልን…” “ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የናይጄሪያና የኢትዮጵያ ጨዋታ…” እያልን ነገር ስናሳምር ከረምንና ጭራሽ ቤተክርስትያን የገባች እንትን ጋዜጠኞች ሆነው አረፉት!
(ለነገሩ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንዶቻችን ጋዜጠኞችም እኮ አለ አይደል…ስናደንቅ ‘ቃላት አመራረጥ’ አልቻልንበትም ነበር፡፡ ቀስ ብለን በምትንቃቃ መሰላል በጥንቃቄ እየተረገጠ እንዲወጣ ከማድረግ ይልቅ መንኮራኩር ውስጥ ከተን እንተኩስና ከዛ ማውረዱ መከራ፡፡
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
ደግሞላችሁ…በስነ ጥበባችን አካባቢ መኮፈስ፣ ‘ማበጥ’፣ ምናምን በሽ እንደሆነ ነው የሚወራው። እናላችሁ…አንድ ፊልም ሲወጣ ለስፖንሰርሺፕ እንዲመችም፣ ለፈረንካውም “መቼም ግሩም የሆነ ፊልም” “ግሩም ትወና” ይባልና ሰዉ ሆዬ ያለክሬንና ያለክንፍ ላይ ወጥቶ ቁብ!
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
እናላችሁ… ያስቸገረን ነገር ኖር ከተሰቀሉበት ማማ ለመውረድ ፈቃደኛ አለመሆን ነው፡፡ አንድ ሰሞን እግር ኳሳችንን  ጄኔቭ ድረስ ሲያሯሩጥ የነበረው… ውረድ እንውረድ ብሎ ነገር የለም፡፡
ደግሞላችሁ…አንዳንድ ምሁራን ዘንድ ብትሄዱ…አለ አይደል… በቤተሰብ ጉባኤ፣ የቢራውን ሂሳብ እንዴት ‘እንደሚያዘጋ’ ዘዴው የገባው… የዓይን መነጽር የሚሰካና የኮቱን ኮሌታ ገደድ የሚያደርግ ሁሉ የአሪስቶትል ደቀ መዝሙር የሚያደርግ ምስኪን ተማሪ… ላይ አውጥተው ያስቀምጧቸውና እንዴት ይውረዱ! “ኧረ እንደ እሱ አይነት ችሎታ ያላቸው መአት አሉ፣ እነሱ እንኳን ላይ ሄደው ሊሰቀሉ አጠገባቸው መሰላልም አሳንሰርም የለም…” ሲባሉ ማን ሰምቶ! ነገርዬው… “እኔን ውረድ የምትሉኝ ማናችሁና ነው…” አይነት ነገር ነው፡፡
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
ሙዚቃ አካባቢ ብትሄዱ… አለ አይደል… አንዱ ዕድለኛ አንድ ሲንግል ይለቅና ምን አለፋችሁ፣ እዚህም እዛም የእሱ ዘፈን ከተማውን ሰቅዞ ይይዘዋል፡፡ ዕድሜ ለኤፍ ኤሞች ምን ችግር አለ! (እኔ እንደውም ከዕለታት አንድ ቀን “ኤፍ ኤም ላይ ‘እንዲህ ተደብቆ የከረመው ድምፀ መረዋ…’ ምናምን የሚሉኝ ከሆነ ሲንግል የማልለቅሳ!” ማለቴ አይቀርም፡፡
እናላችሁ…አንዳንድ ፕሮግራሞች ላይ ስለሆነ ሙዚቃ ወይም ስለ ፊልም ሲወራ ግርም ይላችሁና… “እንደው የሥራው ባለቤቶች የዚሀ አይነት ከመሬት እጅግ ከፍ ብሎ ከመንግሥተ ሰማያት ትንሽ መለስ የሚል አደናቆት ለራሳቸው ይሰጣሉ?” ያሰኛችኋል፡፡
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
አንድ የሆነ የማስቲካም ይሁን የመኪና ማስታወቂያ ላይ ሁለት ቀን ብልጭ ብላ የጠፋች እንትናዬ…በቃ ላይ ወጥታ ጉብ! “ኧረ ቀስ ብለሽ ተራመጅ፣ እንደ ሞዴል ‘ለመነስነስ’ ትደርሽበታለሽ…” ቢባል ማን ሰምቶ! በዚህ ላይ ደግሞ ዙሪያዋን ከበው “አንቺ እኮ የሀበሻ ክሌኦፓትራ ማለት ነሽ…” ምናምን የሚላት አሟሟቂ መአት ስለሆነ ኮከቦቹን ልትነካ ደርሳ ‘ማን፣ ኧረ ማን’ ነው ውረጂ የሚላት!”
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
እናላችሁ… የእልፍኝ አስከልካይ ረዳት እንኳን ሳንሆን እንደ ናፖሊዮንነት የሚቃጣን…አለ አይደል… ላይ አውጥተው ሲሰቅሉን ነው፡፡ ስሙኝማ…ምን ይገርመኛል መሰላችሁ…ሰዋችን ከደግነትም ይሁን፣ “ቲራቲር እንሥራበት …” ከማለት ሲያመሰግንና ሲክብ ምን አለፋችሁ…“አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ…” አይነት ነገር ነው፡፡
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
እናላችሁ፣ ነገርዬው እኮ… አለ አይደል… ሰውን የማይሆን ቦታ አውጥቶ ጉብ ማደረግ፣ ልክ ለራሰ በራ ሰው ለልደቱ የማበጠሪያ ስጦታ እንደመስጠት ነው። አሃ፣ ምን ያደርግለታል… አንደኛውን ጭንቄውን ሊነቀስበት ካልሆነ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
(“ኧረ የራስህ ጭንቄ! ሁለተኛ፣ አይደለም ክትፎና አሮስቶ ዲቢቴሎ ጮርናቄ እንኳን አታገኛትም። ማበጠሪያህን ብላ…” ምናምን የምትሉ ወዳጆቼ ብስጭታችሁ ስለገባኝ ደብዳቤ ሳታስገቡ፣ ኮሚቴ ሳይቋቋም ይቅርታ አድርጌላችኋለሁ፡፡ የቮድካው ተረኛ ማን ነበር!)
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
ስሙኝማ… እግረ መንገዴን… እንደ ድሮ ቢሆን ኖሮ “ጥር የልጃገረድ ጠር…” አበቃ ማለት ነበር! ለነገሩ ጥያቄ አለን… ለጥር ብቻ የተሰጠው ‘የልጃገረድ ጠርነት ለአሥራ ሦስቱም ወራት ይሰጥልንማ! እኔ የምለው…በዛ ሰሞን፣ ‘ያልተነካ’ ምናምን ነገሩ አሥር ሺህ ብር ያወጣል ነው የተባለው! እኔ የምለው…እሱም እንደ ‘ክትፎ’… አለ አይደል… ‘ኖርማልና ስፔሻል’ ነገር አለው እንዴ! አሀ..ማወቅ አለብና! ነገ ድንገት ዲታ ከሆንን ምድረ ሀብታም ሲያደርግ የነበረውን ነገር ሁሉ “ምን የተለየ ነገር  ቢኖረው ነው! ብለን መሞከራችን አይቀርማ!
እግረ መንገዴን…በቀደም አንድ ድረ ገጽ ላይ “ባልና ሚስት መናጠቅ ብሶበታል” ምናምን የሚል ነገር አንብበን ነበር፡፡ አንድ ተረት አለች…
“አገባሻለሁ ያለ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ”
ይሄ እንግዲህ ያኔ መነጠቅ እንግዲህ የሚያስፎክር ባልነበረበት ጊዜ ይባል የነበረ ነው፡፡
ዘንድሮ ግን ነገርዬው ተሻሽሎ ምን ሊባል ይችላል መሰላችሁ…
“ባልሽ ነኝ ያለሽ መወሸሙ ላይቀር፣ የማንን ጎፈሬ ታበጥሪ ነበር”
ቂ…ቂ…ቂ… ‘ግጥም ተገጠመ’ ይሏችኋል እንዲህ ነው!
እኔ የምለው…እንገዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ማስታወቂያው ሁሉ ‘ግጥም፣ በግጥም’ የሆነው…የግጥም ምሽት ስለበዛ ነው እንዴ! ግራ ገባና…አንዳንዱ የማስታወቂያ ‘ግጥም ድርደራ’ እኮ…የድንጋይ ዘመን ትውስታ ነገር ይመስላል። ይሄኔ እኮ የእኔ ቢጤ አሟሟቂ “ፐ! የሠራኸውን ማስታወቂያ ስሰማ እኮ…ምን አልኩ መሰለህ…ይሄ ሰውዬ ኢትዮጵያ ውስጥ መወለድ አልነበረበትም ነው ያልኩት!” እያለ ‘እዛ ላይ’ ሰቅሏቸዋል!
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
ስሙኝማ…ቦተሊከኞችማ አንዴ ካወጧቸው… አለቀ በሉት! ማን ‘እናቱ የወለደችው’ ነው እነሱን ካሉበት ዙፋን ዝቅ ለማድረግ የሚሞክረውስ…አይደለም መሞከር ማንው የሚያስበውስ! ታዲያላችሁ… የአገራችንን መሽቶ ሲነጋ ‘ጠርቶ የማይጠራ’ ቦተሊካችንን ነገሬ ስትሉ የሚያባላን ስር የሰደደ እምነት ምናምን ሳይሆን ይቺ የ‘ውረድ እንውጣ’ ነገር አትመስላችሁም! “በሦስተኛው ዓለም ቦተሊካ ወጣህ ማለት በቃ ወጣህ ማለት ነው!” ብሎ እቅጩን የሚነግረን ሰው እየጠበቅን ነው፡፡ እናላችሁ…ዘላለም “ማን ባሞቀው ወንበር ማን ይቀመጣል፣ ሰማይ ከምድር ይደባለቃል! ” እየተባለ…የምንጨፍረው “ሠላሳ አንድ ዓመት…” ጠብቀን በምንገባባት የኳስ ውድድር ብቻ ሆኗል፡፡
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Published in ባህል

ከንቲባ ድሪባ ኩማና ኮሚሽነሩ መከራከሪያቸውን ለፍ/ቤት ያቀርባሉ
አንድነት፣ የመንግስት አካላትን በተከታታይ እከሳለሁ ብሏል

አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት)፣ የአዲስ አበባ  ከንቲባና የፖሊስ ኮሚሽነራቸው ላይ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሰረተ ሲሆን ተከሳሾች መልሳቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ለየካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
አንድነት ፓርቲ፤ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” የተሰኘ አገር አቀፍ የ3 ወር ንቅናቄ ማጠቃለያን በአዲስ አበባ ባካሄደበት ወቅት በከተማ አስተዳደሩና በፖሊስ ኮሚሽን እስርና ወከባ እንደተፈፀመበት ገልፆ፤ በደላቸውን በማስረጃ በመዘርዘር ክስ መመስረቱን አስታውቋል፡፡
በፖሊስ ተፈፀመ በተባለ በደል ከንቲባውን በቀጥታ ለምን እንደከሰሰ ፓርቲው ሲያስረዳ፣ የአዲስ አበባ መተዳደሪያ ቻርተር ከንቲባው የከተማዋን ፖሊስ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ስለሚደነግግ ከንቲባውን በቀጥታ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል ብሏል፡፡
ቅስቀሳ ላይ የነበሩ የፓርቲው አመራሮችና አባላት በጅምላ በፖሊስ ታስረው መዋላቸውን ፓርቲው ጠቅሶ፣ የቅስቀሳ ቁሳቁስ ተነጥቀናል፤ ፖስተሮችን እንዳንለጥፍ ተከልክለናል ብለዋል። የፖሊስን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የመከታተል ሃላፊነት የተጣለባቸው ከንቲባውና ኮሚሽነሩ፣ የፖሊስን ህገወጥ ተግባር በቸልታ አልፈውታል ብሏል - አንድነት ፓርቲ፡፡
“በቂ ማስረጃ ከተደራጀ በኋላ ነው ወደ ክስ የሄድነው” ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ ክሱን የመሰረቱት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ እና ረዳታቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከንቲባውና ኮሚሽነሩ የካቲት 24 ቀን መልሳቸውን ካቀረቡ በኋላ መጋቢት 2 ቀን ክርክር ይካሄዳል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ፍ/ቤት የለም ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት የፓርቲው መሪዎች፤ የመንግሥት አካላት የሚፈፅሙትን አፈና በይፋ ወደ ፍ/ቤት በመውሰድ የፍትህ ስርአቱን መፈተንና ለህዝብ ማጋለጥ አንዱ የትግል አላማችን ነው ብለዋል፡፡
ከሰኔ እስከ ነሐሴ 2005 ለ3 ወራት፣ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል በመላ አገሪቱ  የተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎች ህዝብን በማነቃቃት ስኬታማ ውጤት አግኝተንባቸዋል ሲሉ የፓርቲው መሪዎች ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በፀጥታው ኃይል እና  በገዢው ፓርቲ ካድሬ መካከል ልዩነት አለመኖሩን አይተናል፤ በአገሪቱ በተዘረጋ የአፈና መዋቅር ከፍተኛ የህግ ጥሰት እንደሚፈፀም አረጋግጠናል ያሉት የፓርቲው መሪዎች፤ የመንግስት ጫና ሳያሸብረው ፓርቲው ተመሳሳይ ንቅናቄዎችን በተከታታይ ያዘጋጃል ብለዋል፡፡  
“የፀረ-ሽብር አዋጁን ለማሰረዝ የሰበሰባችሁትን ድምፅ የት አደረሳችሁት” የሚል ጥያቄ ከአዲስ አድማስ የቀረበላቸው አመራሮቹ፤ “የተሰበሰበውን የህዝብ ድምፅ ወደ ፍ/ቤት ለመውሰድ የህግ ባለሙያዎች እየመከሩበት ነው፣ በሁለተኛ ዙር የክስ ሂደት ውስጥ የሚካተት ይሆናል ብለዋል፡፡ በተካሄደው የ3 ወር የህዝብ ንቅናቄም መንግሥት ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ ፓርቲው ጫና ማሳረፉን የሚያመለክቱ ውጤቶች መታየት መጀመራቸውን የጠቀሱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው፤ የፀረ-ሽብር አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ለህዝብ ውይይት መቅረብ ሲገባው  አዋጁ ወጥቶ ብዙዎችን ሰለባ ካደረገ በኋላ መንግስት ራሱን ለመከላከል የፕሮፖጋንዳና የስልጠና ዘመቻ ጀምሯል ብለዋል፡፡ ይህም ፓርቲያቸው ይዞት የተነሳው ጥያቄ ጫና ማሳረፉንና ትክክለኛ እንደነበር የሚያረጋግጥ መሆኑን አቶ ሃብታሙ ገልፀዋል፡፡
“ማንም ሰው ወይም አካል ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም” ያለው ፓርቲው፤ ህግ በሚጥሱ የመንግስት አካላት ላይ በተከታታይ ክስ እመሰርታለሁ፤ በቅርቡም በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና በገዢው ፓርቲ ላይ ተጨማሪ ክስ ለመመስረት እየተዘጋጀሁ ነው ብሏል፡፡

Published in ዜና

             የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሰሞኑን በሰላማዊ መንገድ ሲንቀሳቀሱ በነበሩት የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት ፓርቲ አባላት ላይ የተፈፀመውን ወንጀል አጥብቆ እንደሚያወግዘው አስታወቀ፡፡
መድረክ በትላንትናው ዕለት “በሰላማዊ አግባብ ሲንቀሳቀሱ በነበሩት የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት አባላት ላይ የተፈፀሙት ወንጀሎች የሀገራችንን ፖለቲካ ከድጡ ወደ ማጡ የሚከቱ ስለሆነ አጥብቀን እናወግዛለን” በሚል ባወጣው መግለጫ፣ ሰሞኑን በትግራይ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ ዞኖች የፓርቲውን አላማና ፕሮግራም በማስተዋወቅ ላይ የነበሩትን የአረና አባላት ገዢው ፓርቲ በተደራጁ ወንጀል ፈፃሚ ቡድኖች ድብደባ እንዲፈፀምባቸው በማድረግ ጥር 18 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲግራት ከተማ ሊካሄድ የነበረውን ስብሰባ ማደናቀፉ እጅግ እንዳሳዘነው ገልዷል፡፡
ፓርቲው ህጋው እውቅና ያለውና በህጋዊ አግባብ የሚንቀሳቀስ መሆኑን የገለፀው መድረክ፤ በህጋዊ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን የፓርቲውን አባላት በተደራጀ ወንጀል ፈፃሚዎች ማስደብደብና ህዝባዊ ስብሰባን ማደናቀፍ የአገራችን ፖለቲካ ወደ ቁልቁለት እየተንደረደረ መሆኑን ማሳያ ነው በማለት አጥብቆ እንደሚያወግዘው ገልጿል፡፡
“እስከ ዛሬ ድረስ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎችና ከተሞች መድረክና አባል ድርጅቶቹ ለማካሄድ ያቀዷቸውን ህዝባዊ ስብሰባዎች በተለያዩ ማስፈራሪያዎችና የቢሮክራሲ ማደናቀፊያ ስልቶች ኢህአዴግ ሲያስተጓጉል ቆይቷል” ያለው መድረክ፤ አፍራሽና ህገ-ወጥ ስልቱን በማባባስ በአዲግራት ከተማ ለህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ ለማድረግ በተሰማሩ የአረና/መድረክ አባላት ላይ ድብደባ እንዲፈፀምና የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጉ እንዳሳዘነው ገልዷል፡፡ “ጉዳዩን ይበልጥ የከፋ የሚያደርገው በአረና/በመድረክ አባላት ላይ ድብደባው የተፈፀመው ህግ አስከባሪ ፖሊሶችና የአካባቢው አስተዳደሮች ባሉበት መሆኑ ነው” ካለ በኋላ፤ በድብደባው አካል ጉዳት ከመድረሱም በላይ እንደ አቶ አሰግድ ገ/ሥላሴና አቶ አብርሃ ደስታ ያሉ የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች በማሳሰር የስብሰባ እቅዱ እንዲደናቀፍ ኢ-ህገ-መንግስታዊ የሆነ አፈናውን በግልፅ መቀጠሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ለትግራይ ህዝብ በፅናት ታግያለው የሚለውን የህውሀት.ኢህአዴግን ማንነት በግልፅ ያሳያል ብሏል መድረክ፡፡ በቅርቡ በአረና አባላት ላይ የተፈፀመው ወንጀልም የሰላማዊ ትግሉን በር የሚዘጋና ኢትዮጵያን ወደ አስከፊ የጦርነት አዙሪት የሚገፋ በመሆኑ አጥብቆ እንደሚያወግዘው ገልፆ፣ “ህዝቡም ይህን ፀረ-ሰላምና ፀረ-ዲሞክራሲ የኢህአዴግ ድርጊት እንዲያወግዝ ጥሪ አስተላልፋለሁ” ብሏል፡፡

Published in ዜና

ዓረና፤ በትግራይ ሁመራ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ፍቃድ ካገኘ በኋላ ወሩ የህወሓት 39ኛ ዓመት የልደት በዓል የሚከበርበት ወቅት ነው በሚል የከተማው አስተዳደር ስብሰባውን እንዳገደበት የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አብርሃ ደስታ ገለፁ፡፡
አቶ አብርሃ ደስታ ለአዲስ አድማስ እንደጠቆሙት፤ ባለፉት ሳምንታት በሁመራ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የሰነበቱ ሲሆን፤ ስብሰባውን ቅዳሜ እና እሁድ እንዳያደርጉ ተከልክለው ለትናንት አርብ ፈቃድ አግኝተው ነበር፡፡ ይሁንና በሰላማዊ መንገድ ህዝባዊ ጥሪ አድርገን ቅስቀሳውን በተሳካ ሁኔታ ከፈፀምን በኋላ በህወሓት የልደት በዓል ተጨናንቀናል፤ የተቃውሞ ስብሰባ ማድረግ አትችሉም፤ ህገወጥ ናችሁ” ተባልን ብለዋል - አቶ አብርሃ፡፡
ህዝባዊ ስብሰባው  በፓርቲው ፖሊሲ፣ በኢትዮ-ኤርትራና ኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ እንዲሁም በአገር ሉዓላዊነት ዙርያ የሁመራን ህዝብ ለማወያየት ያለመ ነበር ያሉት የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባል፤ ኢህአዴግ የተለያየ ምክንያት ይደርድር እንጂ ስብሰባችንን ያስተጓጐለው ፓርቲያችን ስጋት ስለሆነበት ነው ብለዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ፓርቲው በዓዲግራት ስብሰባ ለማካሄድ ቅስቀሳ ሲያደርግ፣ አባላቱ እንደተደበደቡና እንደታሰሩበት አቶ አብርሃ አስታውሰዋል፡፡

Published in ዜና

በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ተፈልገው በጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው የ“ጌታስ ኢንተርናሽናል” ከፍተኛ ባለአክሲዮን አቶ ጌቱ ገለቴን ጨምሮ ሌሎች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች፣ በጥሪው መሰረት ባለመቅረባቸው ፍ/ቤቱ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ሰሞኑን ብይን የሰጠ ሲሆን ችሎቱ የእነ አቶ መላኩ ፈንታን ጉዳይም ተመልክቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ የዋለው ችሎት፤ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ ያስተላለፈባቸው አቶ ጌቱ ገለቴን ጨምሮ የገቢዎችና ጉምሩክ ሰራተኞች  አቶ ታደሠ ፈይሣ፣ ገዳ በሽር እና ነጋ ቴኒ የቀረበባቸው ክስ፤ ከቀረጥና ታክስ መቀነስና ማስቀነስ ጋር የተያያዘ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በእለቱ በቀጠሮአቸው መሠረት ችሎት፣ የቀረቡት፤ የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ እና ምክትላቸው አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ በመዝገቡ የተካተቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች እና ባለሃብቶች፤ የክስ መቃወሚያቸውን ያቀርባሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም አንዳንዶቹ አልደረሰልንም በማለታቸውና ተጨማሪ 10 ቀን በመጠየቃቸው፣ ፍ/ቤቱ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ የሁሉንም ተከሳሾች መቃወሚያ ለመስማት ለየካቲት 10 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
በሌላ በኩል የቀድሞ የደህንነት ኃላፊ በነበሩት በአቶ ወ/ሥላሴ መዝገብ፣ ህገወጥ ሃብት ይዞ መገኘት በሚል የተከሰሱ ተከሳሾች ላይ አቃቤ ህግ ክሴን ላሻሽል በማለቱ ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ለየካቲት 3 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

Published in ዜና

አገሪቱ አዋጆቹን አለማፅደቋ በተመድ የሰብአዊ ምክር ቤት አባል እንዳትሆን አግደዋት ቆይተዋል

ኢትዮጵያ የህፃናት ሽያጭን፣ የህፃናት የወሲብ ንግድንና ህፃናትን በወሲብ ተግባር ማሳተፍን የሚከለክልና ህፃናትን በጦርነት ማሳተፍን የሚያግዱ ሁለት አለም አቀፋዊ የህፃናት መብቶች ኮንቬንሽን አፀደቀች፡፡ አገሪቱ እስከአሁን ኮንቬንሽኑን ካላፀደቁት አስራ አራት የዓለም አገራት አንዷ ሆና ቆይታለች፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን በይፋ ያፀደቀው የኮንቬንሽኑ ፕሮቶኮል እንደሚያመለክተው፤ 162 አገራት ፕሮቶኮሉን አፅድቀው አባል ሆነዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት  ድርጅት (ዩኒሴፍ) ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የህፃናት ሽያጭ፣ የህፃናት የወሲብ ንግድና ቱሪዝም እንዲሁም ህፃናትን ወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች የማሰራት ወንጀሎች በዓለም ዙሪያ እጅግ አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ህፃናት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በሚሰበስቡ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች የወሲብ ንግድ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ ይደረጋሉ ያለው መረጃው፤ በህፃናቱ ላይ ለሚደርሱ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ለዚህ መነሻ ምክንያቱም ኋላቀርነት፣ ድህነት፣ የኢኮኖሚ ልዩነት፣ ፍትሃዊ ባልሆነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መዋቅር የፈረሱ ቤተሰቦች፣ የትምህርት አቅርቦት እጥረት፣ ከገጠር ወደ ከተማ ስደት፣ የፆታ ልዩነት፣ ጎጂ ባህላዊ ልማዶችና ጦርነቶችን እንደምክንያት ጠቅሷል አዋጁ እነዚህን ተግባራት በህግ መከልከልና የህፃናት ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ  ይደነግጋል፡፡
ህፃናትን በጦርነት ማሳተፍን ለመከልከል የወጣው የህፃናት መብቶች ኮንቬንሽን በበኩሉ፤ ሁሉም አገራት ወንዶችንም ሆነ ሴት ህፃናትን በጦርነት እንዳያሳትፉ የሚጠይቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶት ምክር ቤት አባል ለመሆን በተወዳደረችባቸው ጊዜያት ሁሉ ይህንን የህፃናት መብት ኮንቬንሽን ፕሮቶኮል አለማፅደቋ እንቅፋት ሆኗት እንደቆየ የጠቀሰው ለፕሮቶኮል ማፅደቂያ የወጣው መግለጫ፤ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ምክር ቤት የአገሪቱን አጠቃላይ ወቅታዊ ግምገማ ሪፖርት ባቀረበበት ጊዜም አገሪቱ ይህንኑ ኮንቬንሽን እንድታፀድቅ ምክር ሰጥቷት እንደነበርና ግዴታ ከገባችባቸው ጉዳዮች አንዱ እንደሆነም ጠቅሷል፡፡
በአዋጁ አገሪቱ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን በጦርነት እንዲሳተፉና በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ እንዲቀጠሩ አለመደረጋቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነትን የጣለባት ሲሆን አባል አገራቱ 18 ዓመት ያልሞላቸውን ህፃናት በግዳጅ ለወታደራዊ ተግባር እንዳይመለምሉ ግዴታ ይጥላል፡፡  አለም አቀፋዊ የህፃናት መብት ኮንቬንሽኑ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በፀደቀበት ወቅት እንደተገለፀው፤ ኮንቬንሽኑን ለማስፈፀም የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

Published in ዜና

        በዘመናዊ ግንባታ የተነሳ የቀድሞ ስሞቿን እያጣች ነው የተባለችውን መርካቶን ከነስሞቿ ለትውልድና ለቱሪስቶች ለማቆየት ዘመቻ ሊጀመር እንደሆነ ተገለፀ፡፡
መርካቶ ውስጥ ከ50 በላይ የሚጠጉ “ተራዎች” እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡
ባለፈው ረቡዕ መሳለሚያ አማኑኤል ፀጋ ህንፃ ላይ በሚገኘው የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ አስተዳደር ፅ/ቤት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በመርካቶ ከዘመናዊ ግንባታ ጋር በተገናኘ እንደነ ምን ያለሽ ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ቦንብ ተራ፣ ሳጥን ተራ፣ በርበሬ ተራ፣ ያሉ ስሞች ሊጠፉ መቃረባቸው የተጠቆሙ ሲሆን ይህም 75 ዓመት እድሜ ያላትንና በአፍሪካ ትልቋ የገበያ ማዕከል እንደሆነች የሚነገርላትን መርካቶን ታሪክ አብሮ ያጠፋል ተብሏል፡፡ የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤትና ኤርቦሬ ኮሚዩኒኬሽንና ቢዝነስ ፒኤልሲ የመርካቶን ታሪክ ለመታደግ በትብብር የሚያካሂዱት ዘመቻ የካቲት 15 እና 16 እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
ዘመቻው በዋነኝነት የንግዱን ማህበረሰብ በማሳተፍ በሚገነቡ የንግድ ህንፃዎች ላይ የተራዎቹ ስም ከነ ታሪካዊ ምክንያታቸው ተገልፆ በእምነበረድ እንዲፃፍና ለትውልድና ለቱሪስት መስብህነት እንዲተላለፍ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም የክ/ከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሪት አዜብ ገ/ማሪያም ተናግረዋል፡፡
“ለመርካቶ ጌጦቿ ጥንታዊ ስሞቿ” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ዘመቻ ላይ የካቲት 15 ቀን በሜትሮ ሆቴል ሲምፖዚየም እንዲሁም መነሻውንና መድረሻውን ምዕራብ ሆቴል ያደረገ የንግዱ ህብረተሰብና ሌሎች አላማውን የሚደግፉ ግለሰቦች የሚካፈሉበት ሩጫ፣ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን፣ የተመረጡ የመርካቶ አካባቢዎች ጉብኝትና መርካቶ ላይ የሚያጠነጥን ዶክመንተሪ ፊልምና መሰል ፕሮግራሞች እንደተዘጋጁ ታውቋል፡፡
በሁለቱ ቀን ዘመቻ ላይ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር፤ ሚኒስትር ዲኤታዎች፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተወካይ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ተወካይ፣ የክፍለ ከተማው ስራ አስፈጻሚዎችና ሌሎች የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የኤርቦሬ ኮሚዩኒኬሽንና ቢዝነስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ግርማ ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና