Saturday, 15 February 2014 13:00

አሁንም ስለጤፍ…

የሆሊውድ ዝነኞች በጤፍ ፍቅር ተለክፈዋል
“የጎጃም ማኛ”… “የዳላስ ሰርገኛ”… ልንል ይሆን?


ጊዜው የጤፍ ሳይሆን አይቀርም…
መንግስት አወጣው የተባለውና በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች የተሰራጨው የእንጀራ የጥራት ደረጃ፣ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
“እንጀራ ይሄን ያህል ሴንቲሜትር ራዲየስና ይሄን ያህል ግራም ክብደት ከሌላት፣ ስትታጠፍም እንክትክት ካለች… እሷ ከጤፍ ሌላ እህል የተቀላቀለባት ፎርጅድ እንጀራ ስለሆነች ከጥራት በታች ናት!” የሚለው የመንግስት መመሪያ፣ ከወረቀት በሳሳ እንጀራ ለተማረሩ የኔቢጤ ‘ሸምቶ በሊታዎች’ ትልቅ የምስራች መሆኑ አልቀረም፡፡
ይህ መመሪያ፣ ለኛ ለምጣድ አልቦዎች የተስፋ… ለዋዘኞች ደግሞ የተረብ ምንጭ ሆኗል፡፡ እንጀራ ጀርባዋ ልሙጥ፣ ፊትለፊቷም አይናማ መሆን እንደሚገባት የሚደነግገውን ይሄን መመሪያ የሰማ አንድ ተረበኛ እንዲህ አለ አሉ…
“መመሪያው ክፍተት አለበት!... እንጀራ ስንት አይን ሊኖራት እንደሚገባ በግልጽ አያስቀምጥም!”፡፡
የአበሻ እንጀራ በሴንቲሜትርና በግራም የምትለካበት፣ አይኗም የሚቆጠርበት ዘመን መጣ ብለን ሲገርመን፣ እነሆ ጤፍም ከብሄራዊነት አልፋ አለማቀፍ አጀንዳ ሆነች፡፡
ያበሻ ጤፍ ከሰሞኑ የአለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆናለች፡፡ ባለፈው ሳምንት ዘ ጋርዲያን፣ ጤፍ በአለማቀፍ ገበያ ተወዳጅ ምርት እየሆነች መምጣቷንና በኪሎ ከ200 ብር በላይ እየተቸበቸበች መሆኗን አስነብቧል፡፡ የአሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ አገራት ገበሬዎች ጤፍ ማምረት መጀመራቸውንም ዘግቧል፡፡
በዚህ ሳምንት ደግሞ ሃፊንግተን ፖስትን ጨምሮ ሌሎች የአለማችን ታዋቂ ጋዜጦችና መገናኛ ብዙሃን ስለጤፍ ሌላ አነጋጋሪ ዘገባ አውጥተዋል። እንደተባለው ከሆነ፣ ጤፍ በሆሊውድ ታዋቂ የፊልም ተዋንያን ዘንድ ተመራጭ ከሆኑ የምግብ ሰብሎች አንዷ ሆናለች፡፡
እነሆ የጎጃም ማኛ እና የአደኣ ነጭ ጤፍ ብቻ ሳይሆን የቴክሳስ ሰርገኛ የሚባልበት ጊዜ ላይ ሳንደርስ አልቀረንም፡፡ ዘንድሮ ጤፍ በ400 ግራም ከረጢት ታሽጋና ሰባት ፓውንድ የሚል ዋጋ ለጥፋ ወደ ሆሊውድ ሰተት ብላ ገብታለች፡፡
የአለማችንን ታዋቂ ሰዎች የምግብ ምርጫ መዝግቦ ይፋ በሚያደርገው ዝርዝር ውስጥ አዲስ ስም ብቅ ብሏል - ጤፍ! የስፓይስ ገርልስ የሙዚቃ ቡድን አባል የነበረችዋ የታዋቂው እግር ኳስ ተጫዋች ዴቪድ ቤካም ባለቤት፣ ቪክቶሪያ ቤካም በጤፍ ፍቅር አቅላቸውን ከሳቱ ዝነኞች አንዷ ናት። እሷ ብቻም አይደለችም፣ የሼክስፒር ኢን ላቭ መሪ ተዋናይ ጂዋይኔዝ ፓልትሮውም ከጤፍ አፍቃሪዎች አንዷ መሆኗ ነው የተነገረው፡፡
“ኢትዮጵያውያን በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዘመናት አጣጥመው ሲበሉት የኖሩት ጤፍ፣ አሁን በተቀረው አለም የሚኖሩ ብዙዎች ነጋ ጠባ ስሙን የሚያነሱት፣ ለማጣጣም የሚሳሱት አዲስ የምግብ እህል ሆኗል” ብሏል ሃፊንግተን ፖስት ስለጤፍ ባስነበበው የሰሞኑ ዘገባው፡፡
ዘገባው እንደሚለው፣ ጤፍ ብረትን ጨምሮ ሌሎች ለጤና ተስማሚ የሆኑ የንጥረነገር አይነቶችን በውስጧ መያዟ ነው፣ ያበሻ መለያ የሆነች ያገርቤት እንጀራ ከመሆን አልፋ በአውሮፓና በአሜሪካ ተወዳጅ ያደረጋት፡፡
በአገር ቤት ሳለች፣ በአገር ልጅ አንደበት “ሆድ ከመሙላት በቀር ጥቅም የላትም” ተብላ ትንኳሰስ የነበረች ጤፍ፣ እነሆ ያላገሯ ስትገኝ “ማን እንደሷ!” ተብላ መሞካሸት ጀመረች፡፡ የጥራጥሬ ዘር በሙሉ ቢሰለፍ፣ እንደ ጤፍ በካልሺየም የበለጸገ አይገኝም ተብሎ ተመሰከረላት፡፡ አንድ ስኒ ጤፍ 123 ሚሊግራም ካልሺየም ትይዛለች ተባለላት፡፡
ምን ይሄ ብቻ… ይህቺው ገበያ የቆመላት እህል፣ በአብዛኛው በጥራጥሬዎች ውስጥ የማይገኘውን ቫይታሚን ሲ አጭቃ ስለመያዟና በፕሮቲን ስለመበልጸጓ ተነግሮላታል፡፡ ኢትዮጵያውያን በምግብ ከሚያገኙት ፕሮቲን ሁለት ሶስተኛውን የምትሰጣቸው ጤፍ እንደሆነችና ከጀግና አትሌቶቿ ስኬታማነት በስተጀርባ ይህቺው ታሪከኛ ቅንጣት ፍሬ እንዳለችም፣ ዘ ሆል ግሬንስ ካውንስል ሰጠኝ ያለውን መረጃ ጠቅሶ ሃፊንግተን ፖስት ጽፏል፡፡
“ጤፍ እንዲህ ዛሬ ቀን ሊወጣላትና የስነምግብ አጥኝዎችን ትኩረት ልትስብ፣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በተለያዩ አገራት የእንስሳት መኖ ነበረች” የሚለውን የሃፊንግተን ፖስት ዘገባ ያነበበ የኛ አገር ሰው፣ “ምን ያሉት ጡር የማይፈሩ ግፈኞች ናቸው!?” ማለቱ አይቀርም፡፡
የሆነው ሆኖ፣ አሁን ጊዜው የጤፍ ሆኗል፡፡ ጣዕሟና በውስጧ የያዘችው ንጥረነገር ከተመራጭ የምግብ ሰብሎች ተርታ አሰልፏታል፡፡ ፕላኔት ኦርጋኒክስ የተባለው የእንግሊዝ የምግብ አቅራቢ ኩባንያ ባልደረባ የሆኑት ቶቢ ዋትስ፣ ጤፍ በኩባንያው በንጥረነገር የበለጸጉ ጥራጥሬዎች ዝርዝር ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የተሰለፈች አዲሷ የምግብ ሰብል መሆኗን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደንበኞቻቸው ዘንድ እየታየ የመጣው የጤፍ ፍላጎትና ተወዳጅነት፣ ገና ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ አይቀርም ባይ ናቸው፡፡
ፕላኔት ኦርጋኒክስ  ጤፍን በተመለከተ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ጤፍ በተመጋቢዎች ላይ አለርጂ የመፍጠር እድሉ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ ከተመገቡት በኋላም በቀላሉ የሚፈጭ ነው፡፡ ለአጥንት፣ ለቆዳና ለመገጣጠሚያ አካላት ጅማቶች ጤንነት እጅግ ጠቃሚ በሆነው ሲሊካ የተሰኘ የሚንራል አይነት የበለጸገ መሆኑም፣ የጤፍን ጠቀሜታ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከአንድ ሲኒ ጤፍ 286 ካሎሪ፣ 56.8 ግራም ካርቦሃይድሬት እና 8.4 ግራም ፕሮቲን እንደሚገኝም ይሄው መረጃ ያሳያል፡፡
ሃፊንግተን ፖስት እንደዘገበው፣ ጤፍ ተደራራቢ ፕሮቲን ያላቸው የምግብ አይነቶችን ለማይመገቡና ለቬጂቴሪያኖች አሪፍ አማራጭ መሆኑ በጥናት ተደርሶበታል፡፡ እንግሊዛዊቷ የስነምግብ ተመራማሪ አሊስ ማኪንቶሽ ለሃፊንግተን ፖስት እንዳሉት፣ ጤፍ ለጤንነታቸው የሚጠነቀቁ ሰዎች ተቀዳሚ ምርጫ መሆኑ አይቀርም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ተፈላጊነቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ባይ ናቸው ተመራማሪዋ፡፡
የሴትዮዋ አባባል እውነት ሳይኖረው አይቀርም።
ዘ ጋርዲያን ጤፍ በእንግሊዝ ተወዳጅ እሆነ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት በሰራው ዘገባ፣ አንድ ኪሎ ግራም ጤፍ ከ200 ብር በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ እነሆ በቀናት እድሜ ውስጥ፣ ሃፊንግተን ፖስት በሰራው ዘገባ ሌላ የዋጋ ተመን ይፋ አድርጓል፡፡ ዘገባው እንደሚለው አሁን፣ በእንግሊዝ ገበያ 400 ግራም የጤፍ ዱቄት ከ200 ብር በላይ እየተሸጠ ነው ያለው፡፡ ጤፍ ዝናዋ እየናኘ መሄዷን ተከትሎ ዋጋዋም ሰማይ መንካቱ አይቀሬ እንደሚሆንም ዘገባው ግምቱን ሰጥቷል፡፡
እንግሊዛዊቷ የስነምግብና የአካል ብቃት ባለሙያ ፍራንሲስካ ፎክስ እንደሚሉት፣ ጤፍ ለተመጋቢዎች አጠቃላይ ጤና ተስማሚ የሆነ የጥራጥሬ ዝርያ ነው፡፡ “ፊቴን ከአሳማ ስጋ ወደ ጤፍ ያዞርኩትም፣ በአስገራሚ የንጥረነገር ይዘቱ ሰበብ ነው” ብለዋል - ሴትዮዋ ለሃፊንግተን ፖስት ዘጋቢ፡፡
ፕላኔት ኦርጋኒክስ የተባለው የእንግሊዝ የምግብ አቅራቢ ኩባንያ ባልደረባ የሆኑት ቶቢ ዋትስ ግን፣ እንደ ፍራንሲስካ የጤፍን ጸጋ የተረዱና ጤፍ በልተው ማደር የጀመሩ በርካታ ብልሆች ቢኖሩም፣ አሁንም ድረስ ገና የጤፍ ጥቅም ያልገባቸው ብዙ ናቸው ይላሉ፡፡
“አሁንም ድረስ ስለጤፍ ጠቀሜታ በቂ መረጃ የሌላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ጤፍ መመገብ ለጤናማነት የሚያበረክተውን ጠቀሜታ በሚገባ ያልተረዱ በርካቶች አሉ” በማለት ለዴይሊ ሜል የተናገሩት ዋትስ፣ ደንበኞቻቸው ግሉቲን ፍሪ ተብለው ለሚታወቁ ከፍተኛ የንጥረነገር ይዘት ላላቸው ጥራጥሬዎች ያላቸው ፍላጎት እያደገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጤፍም ከነዚህ የጥራጥሬ አይነቶች አንዱ እንደመሆኑ፣ ስለይዘቱ ለደንበኞች በስፋት በማስተዋወቅ ለወደፊት በገፍ እንደሚሸጡት በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
እንኳን ስለጤፍ መረጃ የሌላቸው እንግሊዛውያን፣ ስለጤፍ ይሄንኑ ዘገባ ሰርተው ለህዝቡ ይፋ ያደረጉት የዴይሊ ሜል ጋዜጠኞችም ነገርዪውን በቅጡ የሚያውቁት አይመስሉም፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው ደግሞ፣ ስለ ጤፍ የሰሩት ይሄው የራሳቸው ዘገባ ነው፡፡
“የኢትዮጵያ ዋነኛ ሰብል የሆነው ጤፍ” በሚል መግለጫ ጽሁፍ አጅበው በዘገባው ላይ ያወጡት ፎቶግራፍ፣ የጤፍ ሳይሆን የገብስ ነበር!

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 15 February 2014 12:57

የጥርስ ህመምና መዘዙ

  • የጥርስ ህመም ለልብ፣ ለስኳርና ለሳንባ በሽታዎች ያጋልጣል
  • በስትሮክ የመሞት ዕድልን በእጥፍ ይጨምራል
  • አብዛኛዎቹ የታሸጉ ውሃዎች የፍሎራይድ እጥረት አለባቸው

ያቺ ቆንጆ ጥርሰ በረዶ ናት
ውብ አይናማ ናት
ከዛች ቆንጆ ጥርሷ ከሚያምር
ያዘኝ ፍቅር …
እያለ ድምፃዊው የጥርስን ውበት የገለፀበትን ይህንን ዘመን ተሻጋሪ ዜማ ለዓመታት ደጋግመን ሰምተነዋል፡፡ ዜማው አፍቃሪው የወደዳትን ኰረዳ ውበትና ቁንጅና የሚያወድስበትና ፍቅሩን የሚገልፅበት ቃል አጥቶ፣ ከውበቷ ሁሉ ጐልቶ በታየው የጥርሶቿ ውበት መማረኩን የገለፀበት ውብ ዜማ ነው፡፡ ይኸው ዕውቅ ድምፃዊ የጥርስን ውበት በገለፀበት ሌላው ዘፈኑ ስንኝ ላይ፤  
ይገርማል ቁመናና ዛላ
ልዩ ነው የፀጉሯ ዘለላ
ጥርሶቿ አቀማመጣቸው
ይገርማል አቤት ንጣታቸው …
በማለት ጥርስ ምን ያህል የውበት መገለጫ፣ የውበት ማሣያ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ይህ የውበት መገለጫ የሆነው ጥርሳችን፣ ከሰውነታችን እጅግ ጠንካራው ክፍልና ጠቀሜታው ከፍተኛ የሆነ ተፈጥሮአዊ ስጦታችን ነው፡፡
ጤንነቱ የተጠበቀ ጥርስ ለባለቤቱ ውብ ገፅታን ከማጐናፀፉም በላይ ከሰዎች ጋር ያለ መሳቀቅ ለማውራትና እንደ ልብ ለመሳቅ ያስችላል፡፡ ያለ አፍረትና ያለ መሳቀቅ ለመሳሳምም ጤናማ ጥርስ የሚለግሰው ንፁህ የአፍ ጠረን ወሣኝነት አለው፡፡
ጥርሳችን በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ሊደርስበትና ተፈጥሮአዊ ውበቱን ሊያጣ ይችላል። ለጥርስ ህመም ከሚያጋልጡ በርካታ ምክንያቶች መካከልም ጥርስን በአግባቡ አለማፅዳትና የፍሎራይድ እጥረት ዋንኞቹ እንደሆኑ የጥርስ ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር ይስሃቅ ታምሩ ይገልፃሉ፡፡ የጥርሳችንንና የድዳችንን ጤንነት ለመጠበቅ እጅግ በቀላል መንገድ ጠዋትና ማታ ጥርስን በብሩሽና በጥርስ ሳሙና ማፅዳት እንዲሁም ምግብ ከተመገብን በኋላ አፋችንን በመጉመጥመጥ በጥርሳችን ውስጥ የሚቀሩ የምግብ ትርፍራፊዎችን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡  የጥርሳችንን ጤና ለመጠበቅ ካልቻልን በአለማችን እጅግ አደገኛ የጤና ቀውስ ከሚያስከትሉ በሽታዎች አንዱ ለሆነው የጥርስ ኢንፌክሽን ልንጋለጥ እንችላለን፡፡
ጥርሳችን ከጭንቅላታችንና ከመላው የአካል ክፍላችን ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን ይህ የአካላችን ክፍል ሲጐዳ (ሲታመም) ጉዳቱና ችግሩ ጭንቅላታችንን ጨምሮ በመላው የሰውነታችን ክፍሎች ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የጥርስ ህክምና ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
የጥርስ ኢንፌክሽን በሽታ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ሊከሰትና ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ የሚችል በሽታ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተሩ፤ ምግብ ከተመገብን በኋላ አፋችንን በመጉመጥመጥ በጥርሳችን መሀል የሚቀሩ ትርፍራፊ ምግቦችን የማናፀዳ ከሆነ፣ ለባክቴሪያ መራቢያ ምቹ ሁኔታዎችን እንፈጥራለን፡፡ በርካታ ባክቴሪያዎች በቀላሉ በአፋችን ውስጥ ከተራቡ በኋላ ጥርሳችን እንዲቦረቦር፣ መንጋጋችን እንዲበሰብስና እንዲቆስል በማድረግ ለጥርስ ኢንፌክሽን ሊያጋልጡን ይችላሉ። እነዚህ ባክቴሪያዎች የአፋችን ውስጠኛው ክፍል እንዲቆስልና መጥፎ የአፍ ጠረን እንዲፈጠር ከማድረጋቸውም በላይ የአንገት አካባቢ ቆዳን በመብላት ተጠቂው የመተንፈሻ ቱቦ ችግር እንዲያጋጥመው ያደርጋሉ፡፡ አየር ወደታማሚው ልብና ሳንባ እንደልብ እንዳይደርስ በማገድ ልብ፣ ሣንባና አዕምሮ ላይ ችግር ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ሁኔታም ታማሚው የአየር እጥረት እንዲያጋጥመው በማድረግ ለሞት ሊዳርገው እንደሚችል ዶክተር ይስሃቅ ይገልፃሉ፡፡
አንድ ሰው በጥርስ ኢንፌክሽን በሽታ ሲጠቃ ምንም አይነት ምልክቶችን አያሳይም፤ ችግር እንደተከሰተ በተጠቂው ሰው ላይ የሚታይ የጤና መቃወስ አይኖርም፡፡ በዚህ ምክንያትም በርካቶች ችግሩ መኖሩን እንኳን ሣያውቁ ለከፋ የጤና ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡ በድድ ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችና እብጠቶችን ለመከላከል ሰውነታችን ኢንፌክሽን ተዋጊ ሴሎችን በማመንጨት እንደሚዋጋ የገለፁት ዶክተር ይስሃቅ፤ እነዚህ ሴሎች በሌሎች የሰውነታችን ክፍሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ በድድና በጥርስ ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች በወቅቱ ተደርሶባቸው በቶሎ ህክምና ካላገኙ በድድና በመንጋጋ ጅማቶች ላይ አደገኛ ጉዳት ያስከትላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢንፌክሽኑ የሚፈጠሩ ባክቴሪያዎች በአፋችን በኩል ወደ ውስጣዊ ሰውነታችን ይገቡና ወደ ልባችን በመምራት፣ ልብ ተፈጥሮአዊ ተግባሩን በአግባቡ እንዳያከናውን ሊያደርጉትና ጉዳት ሊያስከትሉበት ይችላሉ ብለዋል፡፡ በጥርስ ኢንፌክሽን የተጠቁ ሰዎች ከሌሎች ጤናማ ሰዎች ይልቅ በቀላሉ በልብ በሽታ ሊያዙ እንደሚችሉ የጠቆሙት ዶክተሩ፤ የድድ በሽታ፣ ስኳርና፣ የሳንባ በሽታዎችም በዚሁ ችግር ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የችግሩ ተጠቂዎች በስትሮክ የመሞት ዕድላቸው ከሌሎች ጤናማ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ እንደሚበልጥም እንኚሁ የጤና ባለሙያ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ለጥርስ ህመም መንስኤነት በዋነኛነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል አነስተኛ የፍሎራይድ ማዕድን ይዘት ያላቸውን ወይንም በቂ ፍሎራይድ ማዕድን ይዘት የሌላቸውን ውሃዎች መጠጣት ነው ያሉት ዶክተሩ፤ ሰውነታቸው በቂ የፍሎራይድ መጠን ሳያገኝ ሲቀር ወይንም የፍሎራይድ ማዕድን እጥረት በሚከሰትበት ወቅት ጥርሳችንም ሆነ ድዳችን ለከፋ የጤና ችግር ሊጋለጥ ይችላል ብለዋል፡፡ ይህም በአብዛኛው የአገራችን ክፍሎች በስፋት እንደሚታይም ዶክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ተጣርተው በፕላስቲክና በጠርሙስ እየተሞሉ ገበያ ላይ የሚውሉ ውሃዎች በአብዛኛው በውስጣቸው የሚይዙት የፍሎራይድ ማዕድን መጠን እጅግ አነስተኛ መሆኑንና አንዳንዶቹም ምንም ፍሎራይድ ማዕድን በውስጣቸው እንደሌለ የጠቆሙት ዶክተሩ፤ ይህም ለጥርስና ለድድ ኢንፌክሽኖችና ለመንጋጋ መቦርቦር በማጋለጥ፣ የከፋ የጤና ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡ ለመጠጥነት የሚገለገልባቸውን የታሸጉ የፕላስቲክ ውሃዎች የማዕድን ይዘት የማየትና የማወቅ ልምዱ እምብዛም ነው ያሉት ዶክተር ይስሃቅ፤ ይህም ህብረተሰቡ የቀረበለትን ሁሉ ያለጥያቄና ያለዕውቀት እንዲጠቀምና ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንዲጋለጥ እያደረገው ነው ብለዋል። እያንዳንዱ ሰው የሚመገባቸው ምግቦችና መጠጦች ምን አይነት ቫይታሚንና ማዕድኖችን በምን ያህል መጠን እንደሚይዙ ማወቅ ይገባዋል ሲሉም አክለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም በተለያዩ ፋብሪካዎች እየተመረቱ ለህብረተሰቡ ጠቀሜታ የሚቀርቡ ምግቦችና መጠጦች ይዘት ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡
የጥርስ ጤና ላይ ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ተገቢ ነው ያሉት ዶክተር ይስሃቅ፣ በየስድስት ወሩ የጥርስን ጤንነት ለማወቅ ወደ ጥርስ ህክምና ተቋማት ጎራ ማለቱ ጠቀሜታው ሰፊ ነው ይላሉ፡፡
በተለያዩ ፋብሪካዎች ተመርተው በተለያ መጠኖች እየታሸጉ ለገበያ የሚቀርቡ ውሃዎች የኢትዮጵያ ጥራትና ደረጃዎች (የተስማሚነት ምዘና ድርጅት) ዕውቅና የሌላቸው መሆኑን ድርጅቱ በትግራይ ክልል ውስጥ እየተመረተ ለተጠቃሚው ከሚደርስ አንድ የታሸገ ውሃ ውጪ ሌሎቹን እንደማያውቃቸው ቀደም ሲል መግለፁ የሚታወስ ነው፡፡

Published in ዋናው ጤና

        የማህበረሰባችንን ወቅታዊ የሞራል ደረጃ ለመለካት አንድ ሀሳባዊ ቀመር እንቀምር፡፡ ይህንንም ቀመር “ሙሶ-ሎጂ” እንበለው፡፡ ይህንን ቀመር በማህበረሰብ ላይ ተፈጻሚ በማድረግ የሚገኘውን አህዛዊ ውጤት ደግሞ “ሙሶ-ሜትሪ” እንበለው፡፡
(ይህ ማለት ፡-አንድ በሙሶ-ሎጂ ቀመር የተጠና ማህበረሰብ የተገኘው አህዛዊ ውጤት  10 ሙሶ-ሜትሪ ፣0ሙሶ-ሜትሪ ወይም ኔጋቲቭ 5 ሙሶ-ሜትሪ ሲሆን እንደማለት ነው)፡፡
ሙሶ-ሎጂ የማህበረሰብን የሞራል ደረጃ ለመለካት እራሱን ሙስናን እንደ ግብአት ይጠቀማል፡፡ ከማህበረሰብ የሞራል ደረጃ ጥናቱ ጎን ለጎንም ሙስኖችንና  ሙሰኞችንም ለማህበረሰብ ከሚያበረክቱት አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ፋይዳቸው አንጻር በልዩ ልዩ ደረጃዎች ይከፋፍላል፣ ይተነትናል፡፡ በሙሶ- ሎጂ ትንታኔ መሰረትም ሙስና እንደ ሙሰኞች ከልማታዊ እስከ ጥፋታዊ ያሉትን ደረጃዎች ይይዛሉ፡፡ ልማታዊም ሆኑ ጥፋታዊ ሙሰኞች ከቅጣት እንደማይድኑ ልብ ይባልልኝ፡፡
የዚህ አጭር ፅሁፍ አላማ የማህበረሰባችንን የሞራል ደረጃ በሃሳባዊው የሙሶ-ሎጂ ቀመር በመፈተሽ ያለንበትን የሞራል ከፍታ አልያም ዝቅታ ለማየት ሲሆን እግረ መንገዳችንንም የሙስና አይነቶችን እና ባህርያትን ከልማት አልያም ከጥፋት ፋይዳቸው አንጻር በሙሶ-ሎጂ ጥበብ በመታገዝ እንመረምራለን፣ እንተነትናለን፡፡
የሙስና ባህሪያት እና ደረጃቸው
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በሙሶ-ሎጂ ጥበብ መሰረት ሙስና ሁሉ ሃጢያት፣ ሙሰኛ ሁሉ ውጉዝ አይደለም፡፡ ሙስና እና ሙሰኞችም ከልማታዊ እስከ ጥፋታዊ ባሉት እርከኖች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ይህንን ስንል በልማዳዊው የሞራል እና ግብረገብ ህግ መሰረት፣ ማንኛውም አይነት ሙስና ውጉዝ እና ፀረ- ልማት እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል፡፡
“ልማታዊ ሙስና”
በሙሶ-ሎጂ ጥበብ መሰረት፣በተለያዩ እርከኖች ላይ ከሚገኙ ሙስናዎች መካከል ይህ የሙስና ደረጃ ለማህበረሰብ ከሚያበረክተው በጎ ውጤት አንጻር ሲመዘን አዎንታዊ (ፖዘቲቭ) ሙሶ-ሜትሪ ውጤትን ያሳያል፡፡
ይህንን ስንል በዚህ እርከን ላይ ያለ አንድ የሙስና ክስተት እና ተሳታፊ ሞሳሽ  ጥቅል ባህሪ በሙሶ-ሎጂ ቀመር ሲሰላ፣ የእለት ተእለት መስተጋብርን ከማሳለጥ፣ ፍትሃዊ የገንዘብ ሽግግርን (ኢ-መደበኛ ቢሆንም ) ከማፋጠን በዘለለ በሞሳሹ እና በተሞሳሹ ማህበረሰብ ላይ የሚፈጥረው ምንም አይነት አሉታዊ ተጽእኖ የለም፡፡ እንዲያውም መደበኛ በሆነው የሞራል ህግ ጭምር ሲመዘን ከመወገዝ ይልቅ ከእለት ተእለት እንቅስቃሴዎች እንደ አንዱ ሊፈረጅ ይችላል፡፡ ሞሳሹም ሆነ ሙስናው ውጉዝ እና እርኩሳን መሆናቸው ተዘንግቶ ለሂደቱ ይሁንታ እና ልዩ ልዩ ገንቢ ስሞች ተችረውት በብዛት ሲዘወተርና  አገልግሎትን ሲያሳልጥ ይስተዋላል፡፡
በዚህ ማእቀፍ ውስጥ የተካተቱ ሙስናዎች በሂደታቸው ማለትም ከጅማሬያቸው እስከ ፍጻሜያቸው ምንም አይነት ተጎጂ (ከሳሪ) የማህበረሰብ ክፍል የለም፡፡ ይልቁንም የየእለት መስተጋብርን በማሳለጥ በመደበኛው ህግ የተፈጠሩ ክፍተቶችን በመሙላት፣ ለልማታዊ ጉዞአችን ጠቃሚ እሴትን ይጨምራሉ፡፡ በዚህ የሙስና እርከን  ውስጥ የሚመደቡ ሙስናዎች እጅግ ብዙ ቢሆኑም የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና  በየእርከኑ የተቀመጡ ፈጻሚዎች (የስራ ሂደቶች)፣ እየዳበረ በሄደው የግንባታ ዘርፍ ላይ ያሉ ልዩ ልዩ ባለሙያዎችና መሰል ተቋማት አይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ምሳሌ እንጥቀስ፡- ሙስና እንደምን ልማታዊ ሆነ?
ወደ አንድ አንድ መንግስታዊ የአገልግሎት ሰጪ ተቋም ጉዳይ ኖሮን ሄድን እንበል፡፡ በ BPR አልያም በካዘይን ከተገነባው ተቋምና ከባለስልጣናቱ የምናገኘው መስተንግዶና  ትብብር ግን በኢቴቪ እንደምናየው አሊያም በአዲስ ዘመን እንደምናነበው ምቹ እና አልጋ በአልጋ ላይሆን ይችላል(አንዳንዴ ሊሆንም ይችላል)ጉዳያችንን ከውነን ወደ ስራችን በፍጥነት ለመመለስ ግን በሌላ የተሻለና  በሂደት በዳበረ ስውር ህግ ውስጥ ማለፍ ግድ ነው፡፡ በተለያየ እርከን ላይ ላሉ ሹሞች  ኪሳችንና  ዝምድናችን አንደፈቀደ የወጉን ልንል ግድ ይለናል፡፡
ለዚህ ሂደት ያወጣነውን መሞሰሻ ከአገኘነው ፈጣን ውጤት አንፃር ስንመዝነው፣ አትራፊ ከመሆናችን በተጨማሪ በስውር ከተዋቀረው የሙስና ማህበረሰብ አባላት ክብርን፣ባወጣነው መሞሰሻ ለጎንዮሽ  ተጠቃሚዎች መዋጮን እንቸራለን፤አገልግሎት እናሳልጣለን፤የገንዘብ ዝውውሩን ተደራሾች አድማስ በማስፋት የተከሰተውን የኑሮ ውድነት በመዋጋቱ እርብርብ ላይ የበኩላችንን በመወጣት በልማታዊው ሙስና ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንሆናለን ይለናል - ሙሶ-ሎጂ፤ ልማታዊ ሙስናን እና አዎንታዊ መስተጋብሩን በምሳሌ ሲያስረዳን፡፡
ማሳሰቢያ፡- “ልማታዊ ሙስናም” ቢሆን ከተጠያቂነት ነፃ አያወጣም፡፡
ጥፋታዊ  ሙስና
ይህ የሙስና ደረጃ ከልማታዊው ሙስና በተቃራኒው እረድፍ ላይ ሲገኝ በሙሶ-ሎጂም ይሁን በልማዳዊው የሞራል ህግ ሲመዘን ፍፁም አጥፊ፣ የማህበረሰብ ነቀርሳ እና ሲከፋም በዘመንኛ ስሙ “አሸባሪ ሙስና” ሊባል እና ሊፈረጅ ይችላል። በዚህ የሙስና እርከን እና ባህሪ ላይ የትኛውም የፖለቲካ፣ የእምነት አልያም የባህል አባል ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖረው በእኩል ድምጽ ያወገዘው ፀረ-ልማት፣ኪራይ ሰብሳቢ፣ሃራም እና ውጉዝ ሲሆን ሙስናው እና ሞሳሹም የታዩበት የማህበረሰብ ክፍል ከሚደርስበት የልማት ሳንካ ይበልጥ እንደማህበረሰብ የመቆሙ ጉዳይ አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ በእኛው ሃሳባዊ ቀመር ሙሶ-ሎጂም ከዜሮ በታች ኔጌቲቭ ሙሶ- ሜትር ውጤት ያስመዘግባል፡፡
በሙሶ-ሎጂ ቀመር ትንተና መሰረት፣የአንድ ጥፋታዊ ሙስናና  በስሩ የሚዋቀረው ስውር የሙስና ሰንሰለት (ማህበረሰብ )የሚፈጠሩት በሁለት ዓይነት ሂደቶች ነው፡፡ እነርሱም፡-
ከየትኛውም እርከን ላይ ተነስተው የልማታዊ ሙስና ኡደታቸውን ጨርሰው ፍጹም አፍራሽ (ኢ-ልማታዊ) ወደሆነ የሙስና ደረጃ ከሚለወጡ አዳጊ የሙስና አይነቶች  እና፤
ከጅማሬያቸው እና ባህሪያቸው ፍጹም አጥፊ እና የነቀርሳ ባህሪን ከተላበሱ ሙስኖች  ነው፡፡
በጊዜ ሂደት ወደጥፋታዊ ሙስናነት የሚለወጡ ኡደታዊ ሙስኖች
 የእነዚህ የሙስና አይነቶች መነሻ በየትኛውም ሙስና እርከን ላይ ካሉ እና በእድገት ሂደታቸው ጫፍ ላይ ሲደርሱ ከጉዳት አልባነት አልያም ከልማታዊ ሙስናነት ጀምረው የልማት ሳንካ ከመሆን ባሻገር  ለማህበረሰብ ውድቀት ጉድጓድ ቆፋሪዎችና የሞራል ዝቅጠት አመላካቾች የሚሆኑ የሙስና አይነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የሙስና አይነቶች  በለውጥ ሂደታቸው ወቅት ለመሞሰሻ የተተመነው ገንዘብ አልያም ሌላ ተመጣጣኝ ክፍያ በፈጣን ሁኔታ ጭማሪን በማሳየትና በሙስናው አፈፃጸም ሰንሰለት ውስጥ ተሳታፊ አባላቱን በከፍተኛ ፍጥነት በማሳደግ እንዲሁም ተቋሙን በመውረር የተሞሳሹን ጥሪት እስከማሟጠጥ ይደርሳል፡፡ በአጭር ግዜ ውስጥም ስውር የሙስናው ህግጋቶች  የመንግስትና  የህግ አካላትን ትኩረት እስኪስቡ ድረስ በጠራራ ጸሃይ የሚፈፀሙና መደበኛውን አሰራር ተክተው የሚከወኑ የካንሰር ባህሪን የሚጋሩ ሙስና አይነቶች ናቸው፡፡
የእነዚህ ሙስኖች ሌላው አይነተኛ መገለጫቸው በሙስና ሰንሰለቱ ጫፍ ላይ ለሚገኙ ጥቂት ባለስልጣናት (ጉምቱ ሙሰኞች) ኪስ ማደለቢያነት በማገልገል የተቋሙን አገልግሎት እና የማህበረሰብ ተደራሽነት በማቀጨጭ እንዲሁም በነፃው የአገልግሎት ገበያ ላይ አርቲፊሻል የአገልግሎት እጥረትን በመፍጠር፣ የብዙሃን መጉላላትንና  ምሬትን በመከሰት፣ በእድገት ጅማሬያቸው ላይ ከነበራቸው ልማታዊ ባህርይ ወደ ጥፋታዊ ሙስናነት በፍጥነት ይመነደጋሉ ፤የሙሶ ሜትሪ ውጤታቸውም በፍጥነት ወደ ኔጌቲቭ  ያሽቆለቁላል፡፡
ሙስና፤ ሞራል እና ሙሶ-ሎጂ
   ከላይ እንደተመለከተው በሙሶ-ሎጂ ቀመር በመታገዝ  የሙስና አይነቶች እና ባህሪያቸው፤ ከልማት ጋር ያላቸውን መስተጋብር በወፍ በረር ለመቃኘት ተሞክሯል፡፡ በመቀጠልም ወደ አብይ ጉዳያችን እና የሙሶ-ሎጂ አንዱ እና ተወዳጅ ዘርፍ እናምራ፡፡ ይህ ዘርፍ የአንድ የተመረጠ ጥፋታዊ ሙስናን እና ፈጻሚ ሙሰኞችን  ባህሪ በማጥናት ሙስናውን እና ሞሳሹን  ስለቀፈቀፈው ማህበረሰብ የሞራል ደረጃ እንዲሁም የማህበረሰቡን መጻኢ እጣ ፈንታ የሚተነትን እና የሚተነብይ  የሙሶ-ሎጂ ንኡስ ዘርፍ ነው፡፡
በዚህ ቀመር መሰረት፣ የአንድ ጥፋታዊ ሙስና እና ተዋናይ ሞሳሽ የሞራል ዝቅጠት እንዲሁም ይህንን ሞሳሽ  ያፈራን ማህበረሰብ የሞራል ደረጃ እና የማህበረሰቡን እጣ ፈንታ ይተነትናል። ይህንንም ለማስላት አንድ የተመረጠ ጥፋታዊ ሙስና የተፈጸመበትን ግዜ (T1) እና የሙስናው አሉታዊ ውጤት የታየበትን ግዜ ደግሞ (T2) ብንላቸው በሁለቱ ሰአቶች መካከል ያለው የግዜ ልዩነት በጠበበ መጠን ማለትም (T1 - T2 ) ወደ ዜሮ በቀረበ መጠን የሙስናው ጥፋታዊነት (ሀ) እየጨመረ የሙሰኛው የሞራል ደረጃ (ለ) እየወረደ ይመጣል- ይለናል ሙሶሎጂ በዚህ ንኡስ ዘርፉ፡፡ ይህንን ጽንሰ ሃሳብ ወደ ሂሳባዊ ቀመር (ፎርሙላ ) በመለወጥ የተመረጡ እና በማህበረሰባችን ውስጥ የተከሰቱ ምሳሌ ሙስኖችን በዚህ ቀመር (ፎርሙላ ) በመፈተሸ አንድ ሙከራ እንስራ ፡፡
በመጀመሪያ ዋናውን ቀመር ከነባራዊ እውነታዎች እና ሂሳባዊ መሰረታውያን በመነሳት እናዋቅር፡፡
(ማሳሰቢያ፤- ለሂሳብ እና ሂሳብ ነክ ትምህርት ባለሙያዎች የዚህ ቀመር አመጣጥ ቀላል እና ግልጽ ሲሆን ለሂሳብ እና ቁጥር አለርጂኮች  ደግሞ ትንታኔውን መገንዘብ ብቻ በቂ ነው)
 ቀመር (ፎርሙላ) 1.–––––––––––
  ቀመር(ፎርሙላ) 2----------------------
በቀመር 1 ላይ እንደምንመለከተው የሙስናው የጥፋት መጠን (ሀ) እና በሙስናው ጥንስስ እና ፍጻሜ መሃል ያለው የግዜ እርዝመት (T1 - T2 )  ተገላቢጦሽ ተዛማጅ (inversely proportional) ሲሆኑ በቀመር ሁለት ላይ ደግሞ የሙሰኛው የሞራል ደረጃ (ለ) እና በሙስናው ጥንስስ እና ፍጻሜ መሃል የለው የግዜ እርዝማኔ (T1 - T2 ) መሳ ለመሳ ተዛማጅ  (directly proportional) ናቸው፡፡
ከላይ የተመለከቱትን ሁለት ቀመሮች በማዋሃድ ሌላ ከ (ሀ) እና ከ (ለ) አንፃር የተዋቀረ ሶስተኛ  
የሚል ቀመር እናገኛለን፡፡ ይህ ቀመር ደግሞ የሞሳሹ የሞራል ደረጃ (ለ) እና የሙስናው የጥፋት መጠን(ሀ) ተገላቢጦሽ ተዛምዶ እንዳላቸው ያሳየናል፡፡ ይህ እውነታ በቀላል አማርኛ ሲገለጽ  አንድ የሞራል ደረጃው እጅግ የወረደ ሙሰኛ  እጅግ ፈጣን እና ከባድ አጥፊ ሙስናን ያደርሳል በማለት እውነታውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ቀመር 3

እና ምን ይጠበስ ለሚሉ
ከላይ የተዘረዘሩትን ምሁራዊ ዲስኩሮች እና ሃሳባዊ ሂሳባዊ ቀመሮች  ለዩኒቨሪሲቲዎቻችን የማህበረሰብ ሳይንስ ምሁራን ቀጣይ ጥናት እንደመንደርደሪያ በመተው
(የሃሳቡ እና የቀመሮቹ ቀማሪ የባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ)፣
አንዳንድ በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ የተፈጸሙ አጥፊ ሙስኖችን በቀመርነው ቀመር በመታገዝ፣ የማህበረሰባችንን የሞራል ዝቅጠት፤ የአንዳንድ ሙስኖችን ከክፋታዊ ሙስናነት የዘለለ የከባድ ውንብድና ጫን ሲልም የዘር ማጥፋት ወንጀልነት ባህሪን ከሙሶ-ሜትሪ ውጤታቸው በግልጽ ለመመልከት ነው፡፡
ምሳሌ 1- በፍትህ ተቋማት የሚፈጸሙ ሙስኖች፤-
የእነዚህ የሙስና አይነቶች ውጤት በሞሳሹ ላይ በፍጥነት በመፈጸም፣ ህግን በማጣመም ተበዳይን ለከፋ እንግልትና ፍትህ እጦት ሲዳርጉ፣ የሚከወኑትም የሞራል ደረጃቸው በወረደና  የፍትህ እጦት በማይገዳቸው ምግባረ ብልሹ ሙሰኞች ነው።

ምሳሌ -2
በህክምና ተቋማት የሚፈጸሙ ሙስኖች፤- የእነዚህ ሙስኖች የሙስና ውጤት በአጭር ግዜ ውስጥ በህክምን ፈላጊው (ተሞሳሹ) ላይ የሚታይ ሲሆን በውጤታቸውም የከፋ የጤና መቃወስንና ፈውስ ማጣትን በተሞሳሹ ላይ ያስከትላሉ፡፡
ፈጻሚዎቹም በሰው ጤናና  ህይወት ላይ ቁማር በመጫወት ቢዝነስ የሚያጧጡፉ የሞራል ደረጃቸው በምሳሌ 1 ከተጠቀሱት ሞሳሾች እጅግ የወረደ እና የሙስናቸው አሉታዊ ውጤትም እጅግ የፈጠነ ብልሹዎች ናቸው፡፡

ምሳሌ 3- ይህ የሙስና አይነት ልዩ እና ምናልባትም በኢትዮጵያውያን ሙሰኞች ብቻ በኢትጵያውያን ላይ የሚፈፀም የማህበረሰባችን የሞራል ዝቅጠት ዓይነተኛ ማሳያ ሲሆን ሙስናው የሚፈጸመው ምግብ እና የምግብ ውጤቶችን ጥራት ሆን ብሎ በማጓደል ፤ ባእድ እና መርዛማ ነገሮችን ቀይጦ በመሸጥ ወገንን እና   የገዛ ቤተሰብን በመመረዝ፣ ገንዘብ ለማካበት በሚደፍሩ ሞራለ-ዝቃጭ ሙሰኞች (አሸባሪዎች) ነው፡፡  ይሄ የሙስና ዓይነት ጸያፍ እና ውጤቱም በፍጥነት የሚታይ ነው።  

ምሳሌ 4- ይህ የሙስና አይነት በሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም በሰብአዊ ፍጡርና  በሰብአዊ ታሪክ መፈጸሙን እርግጠኛ አይደለንም። የሙስናው  ወንጀል የሚፈጸመው (በእርግጠኛነት መፈጸሙ በማስረጃ ባይደገፍም) የእሳት አደጋ በተነሳበት አካባቢ  ሲሆን ሙሰኞቹም የእሳት አደጋ አጥፊ አባላት ናቸው፡፡
ተሞሳሹ ደግሞ ንብረቱ፣ ልጁ አልያም ሌላ የቅርብ ቤተሰቡ በሚንተገተገው ሰደድ የተከበበበት እና በጣር የተያዘ ግለሰብ ነው፡፡
(ማሳሰቢያ፤-የዚህ የሙስና አይነት ሲፈጸም በአይኔ ያልተመለከትኩ ቢሆንም የሙያውን ስነምግባር የተላበሱና  ህይወታቸውን መስዋእት እስከማድረግ የሚተጉ ምስጉን አባላትን ግን ተመልክቻለሁ)
ከላይ በምሳሌው የተገለጹት  ሙስኖች እና ሞሳሾች ከማህበረሰብ ጠንቅነታቸውና ከፈጻሚያቸው  የሞራል ደረጃ እንዲሁም በሚያስመዘግቡት የሙሶ-ሜትሪ ውጤታቸው አንጻር በቅደም ተከተል ከላይ ወደታች ለማስቀመጥ ከሙስናው ጅማሬ እና በሙስናው ውጤት መሃል ያለውን የግዜ እርዝማኔ
(T1 - T2 ) እንደማወዳደሪያ የተጠቀምን ሲሆን ፤የዚህ የግዜ እርዝማኔ አሽቆልቁሎ በሰደድ እሳት ተከቦ የሽራፊ ሰኮንድ እድሜን በሚጠብቅ ምስኪን ጨቅላ ህጻን እና ሊውጠው በሚወነጨፍ ሰደድ እሳት መሃል በቀረች የእድሜ ቅጽበት መሃል ከሚከወን የሙስና ደረጃ ላይ እንዲሁም ይህንን አጋጣሚ እንደ መልካም የቢዝነስ እድል ለመቁጠር በቂ የሞራል ዝቅጠት ካለው ሙሰኛ ዜጋ ላይ ደርሰናል፡፡
ይህንን ሙስና ለመፈጸም የሚያስችል የሞራል ዝቅጠት ባለቤት የሆነ ሙሰኛና ይህ እንዲሆን ኮትኩቶ ያሳደገ ማህበረሰብ ስንተ ሙሶ-ሜትር ይመዝናል? በዚህ ደረጃ ካለ የሞራል ዝቅጠት ጋርስ እንደ ማህበረሰብ እና ሃገር ምን ያህል እርቀት እንጓዛለን?


Published in ህብረተሰብ

         በ፲፭፺፪ ዓ.ም ግድም የተወለደው ዘርአ ያዕቆብ የጠየቀው ጥያቄ ነው ይህ “ሰዎች ስለምን ይዋሻሉ?” ብዬ አሰብኩ።” ዘርአ ያዕቆብ ጽኑ የምርምር መንፈስ ውስጥ ሁኖ ይኼንን ጥያቄ ያምሰለስላል። “ምናልባትም የሚያገኙት አንዳች ጥቅም ሊኖራቸው ይችላል፤ አሊያም ከሰዎች ዘንድ ከበሬታን እናገኛለን ብለውም ያስቡ ይሆናል” ባይ ነው ዘርአ ያዕቆብ። “ወሐሳዊ ብእሲሰ ዘየኀሥሥ ንዋየ አው ክብረ በኀበ ሕዝብ ለእመ ይረክብ ዘንተ በፍኖተ ሐሰት ይትናገር ሐሰት እንዘ ያስተማስሎ ጽድቀ።” ለዘርአ ያዕቆብ የገንዘብ ፍቅርና /ከንቱ ውዳሴ/ ከፍተኛ የስህተት ምክንያቶች ናቸው፤ ምክንያቱም ቁልቁል በሐሰት ጎዳና ያንደባልሉናልና። ውሸቱን እውነት አስመስለው እያወሩ፣ ክብርንና ገንዘብን ለማግኘት ይቋምጣሉ ይለናል።
ክርስቶስ የተፈተነባቸው የኃጢያት ዋናዎች የሚባሉት ፍቅረ ንዋይ (የሥልጣን ፍቅር፣ከንቱ ውዳሴ)፣ ትምክህት እና ስስት ናቸው። እነዚህ ምግባራት የስህተቶች ሁሉ አለቆች እንደሆኑ ተደርገው ይታሰባሉ፤ በኢትዮጵያዊያን ጥንታዊ ባህል። አንዳንዶቻችን እውቀቱ ሳያንሰን ንባቡ ሳይጎድለን፣ ከእነዚህ መርዛም ማሰናከያዎች መጠበቅ ይሳነን እና ቁልቁል የሐሰትን ጎዳና እንደባለላለን። ብዙዎች ለኑሯቸው የሚያስፈልጋቸውን ወጭ ለመሸፈን ሲሉ የማያምኑበትን ሥራ እየሰሩ፤ ʽለምን የማታምንበትን ሰራህ ሲባሉ “ምን ይደረግ? የኑሮ ጉዳይ ነውʽ ይላሉ። በመጠኑ መኖር ሲቻል ገንዘብ ካገኘሁበት ምን ቸገረኝ የሚባለው ጉዳይ እዚህ ጦስ ውስጥ ይከትታል። የሥልጣን ጉዳይን መቼም ነጋሪ አያስፈልገንም፤ ይኸው እለት እለት ይጠብሰናል። ስስት ዛሬ ላይ መልኳን ቀይራ መንገድ ቅድሚያ ለመሰጠጣጠት እንኳን ፋታ የማታስገኝ ሆናለች። ዘርአ ያዕቆብም “ለሰዎች ለምን ይዋሻሉ?” ጥያቄ የሰጠው ምላሽ፣ ከኃጢያት ዋናዎቹ ካልናቸው ጋር ተመሳሳይ ነው (ኢትዮጵያዊ አይደል እርሱስ)።
ከዛሬ አራት መቶ አመት ግድም የኖረውን ዘርአ ያዕቆብን በስድስት ʽግልብʽ መሞገቻ ሐሳቦች ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ውስጥ ለሚከትቱ ሰዎች ምላሽ ማቅረብን ወደድኩ።
፩) ለሦስት ወር ዳዊት፣ ለአራት አመት ቅኔ እና ለአስር አመት ደግሞ የመጽሐፍትን ትርጉም ተማርኩ ይለናል የአክሱሙ ልጅ ዘርአ ያዕቆብ። እንግዲህ ይታያችሁ… በአብነት ትምህርት ከውሻ እና  ከችጋር (እከክ) ጋር እየታገለ ከአስራ አራት አመት በላይ መከራውን የሚታገስ ኢትዮጵያዊ ካልሆነ በስተቀር ማንም እንዳልሆነ ታሪካችን ምስክር ነው። ገና ከጅምሩ እድሜዬ ለትምህርት እንደ ደረሰ አባቴ ለመምህር ሰጡኝ ሲለን እኮ፣ የዛኔዋን ኢትዮጵያን ባህል እንጅ፤ አውሮጳማ ʽዘመናዊʽ ትምህርትን ከጀመረችው ሰነባብታለች።
፪) «ወጥንተ ሙላድየሰ እምካህናቲሃ ለአክሲም። ወባእቱ ተወለድኩ አነ ተወለድኩ እም፩ ነዳይ መስተገብር ውእተ አድያመ አክሱም።» ዘርአ ያዕቆብ በቀላል ግዕዝ ስለ ራሱ ውልደት እና ዘር እንዲህ ነው የገለጠው። ከካህናት ዘር ከደሃ ቤተሰብ፣ በአክሱም ከተማ ተወለድኩ እንደ ማለት ነው ትርጉሙ። እንግዲህ ዘሩን ከካህን የሚጠቅስ አክሱም የሚወለድ የደኃ ልጅ የሚሆን ሮማዊ/አውሮጳዊ ከተገኘ እሰየው ነው። ግን ይኸም ኢትዮጵያዊ ለሆኑት እንጅ ለማንም አይቻልም።
፫) የዘርአ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡት አንዳንድ ሰዎች፣ የሃሳቡን አደረጃጀት እና አቀራረብ ከአውሮጳዊያን በማመሳሰላቸው የተነሳ ነው። ነገር ግን የዘርአ ያዕቆብን የሐሳብ ክረት (ጥንካሬ) ብናየው፣ በየቅኔ ቤቱ ከሚነሱ ሙግቶች ጋር ሲወዳደር ʽእዚህ ግባʽ የማይባል ሆኖ እናገኘዋለን። ይህም ዘርአ ያዕቆብ እንኳን ከኢትዮጵያዊያን ፍልስፍና በልጦ ሊያስንቅ እና የባዕድ ሰው ነው ሊያስብለው ይቅርና በየቅኔ ማህሌቱ መድረክ ሊያሳጣው የሚችል ጉዳይ ነው። ነገር ግን እንደ ካናዳዊው ፕሮፌሰር ክላውድ (ገላውዴዎስ) ሰምነር የመሰሉ በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ እድሜያቸውን የፈጁ ተመራማሪዎች፣ የዘርአ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊነትን ጥያቄ ውስጥ አያስገቡትም።
፬) ሌላው አስገራሚው ጉዳይ ዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ባይሆን ኖሮ (አውሮጳዊያን ካቶሊካዊያን ስለሆኑ) እንዴት እነ ዮሐንስ ካቶሊካዊ ከሆነው ከንጉሥ ሱስንዮስ ጋር አጣልተውት  ወደ ዋሻ ይሄዳል፤ ሰዎቹ እንደ ሚሉት አውሮጳዊ ቢሆን ኖሮ ʽወደ ቀይባህር ሸሸሁʽ አይልም ነበር እንዴ?
፭) ዳዊቱን አንግቦ መሰከዱ ፍጹም ኢትዮጵያዊ መሆኑን ያሳያል፤ ምክንያቱም በባህላዊ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ መዝሙረ ዳዊት እራስንም፣ሃገርንም፣ቤተሰብንም መጠበቂያ የጸሎት መጽሐፍ ነውና። ምንም እንኳን በቃላችን ብናጠናው ከስህተት እና ከግድፈት ለመዳን ፊደሉን ከመጽሐፉ እያነበቡ መጸለይ ልማድ ነው። s
፮) ለብዙዎች ፈረንጆች ያሳደዱት መነኩሴ እመስላቸው ነበር፤ ይለናል ዘርአ ያዕቆብ። ይህንን የሚለን ከስደቱ ከተመለሰ በኋላ ነበር። ዘርአ ያዕቆብ ከስደት የተመለሰው ሱስንዮስ ከሞተ በኋላ ፋሲል ከነገሰ በኋላ መሆኑ ይታወቃል። በፋሲል ዘመን ደግሞ በታሪክ እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያ ሁሉንም ፈረንጆች አባርራ በሯን ሁሉ ለባእዳን የዘጋችበት ዘመን ነበር። ይህ ከሆነ እንዴት አውሮጳዊው ዘርአ ያዕቆብ በፋሲል ዘመን በሰላም ከዋሻ ወጥቶ እንፍራንዝ ውስጥ ሊኖር ቻለ? ከእርሱ አንደበት እስኪ እንስማ፦ «ወበ፲፻ወ፮፻ወ፳፭ {1625} አመተ እምልደቱ ክርስቶስ ሞተ ሱስንዮስ ንጉሥ ወነግሠ ወልዱ ፋሲለደስ ህየንቴሁ ወውእቱሰ አፍቅሮሙ ቅድመ ለፈረንጅ በከመ አቡሁ ኢሰደዶሙ ለግብጻዊያን ወኮነ ሰላም ውስተ በሐውርተ ኢትዮጵያ። አሜሃ ወጻእኩ እምግብየ ወሖርኩ ቅድመ በሐውርተ አምሐራ…» እግዜር ያሳያችሁ፤ሰ እንግዲህ ፈረንጆች እና ሱስንዮስ ተባብረው ብዙ ኢትዮጵያዊያን መነኮሳትን እና የሃይማኖት አባቶችን ካሳደዱና ከገደሉ በኋላ ፋሲለደስ ነገሰ (ሃይማኖት ይመለስ፤ ፋሲል ይንገስ የሚለውን መፈክር አስታውሱ)። ፋሲል ሲነግስ ሃይማኖት ተመለሰ፤ የተሰደደ መነኩሴም የሃይማኖት አባትም ወደየ ገዳሙና አጥቢያው ተመለሰ። ይህንን ዜና የሰማው ድንጉጡ ዘርአ ያዕቆብ ከዋሻው ወጣና ወደ ጎጃም መጓዝን ፈለገ ነገር ግን መንገድ ላይ እንፍራንዝ ሲደርስ ለነፍሱ የሚስማማው ቦታ እግዚአብሔር አመላከተው እና አቶ ሀብቱ ቤት ተጠለለ። እንፍራንዝ እስኪደርስ ድረስ ግን በየመንገዱ ስደተኛ መነኩሴ እየመሰላቸው ሰዎች ሁሉ ያዝኑለት እንደነበረና ልብስና ምግብ ይሰጡትም እንደ ነበር ይተርክልናል።
እንዴው ለመሆኑ ብራና ዳምጦ ቀለም በጥብጦ መጽሐፍ የሚጽፍ የአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን አውሮጳዊ እንዴት ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኘ። ዘርአ ያዕቆብ ግን ኢትዮጵያዊ ስለሆነ እንዲህ ይለናል። «ወበህዳጥ መዋዕል አስተዳለውኩ ቀለመ ወሰሌዳ ወጸሐፍኩ ፩ደ መጽሐፈ ዘመዝሙረ ዳዊት ወእግዝእ ሀብቱ ወኩሎሙ እለ ርእይዋ ለጽሕፈትየ አንከሩ እስመ ሠናይት ይእቲ።»
መዝሙረ ዳዊትን በብራና የሚጽፍ፤ ከዚያም ሲያልፍ የእጅ ጽሕፈትህ ታምራለች እየተባለ መንደሩ ሁሉ ጻፍልን እያለ የሚማጸነው ሮማዊ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ማግኘታችን በእውነት አዲስ ታሪካዊ ግኝት የሚያስብል ነው። በታሪካችን እንደምናውቀው የፈረንጅ አስተማሪዎች ውሏቸው ከመኳንንቱ ከሹሟሙንቱ ጋር እንጅ እንደው እንዳልባሌ እንፍራን ውስጥ የአቶ ሀብቱ ባሪያን (አገልጋይ)አግብቶ የገጠር ከተማ ውስጥ መኖር እንዴት ይቻለዋል።
በዚያ በአውሮጳዊያን ዘመነ አብርሆት አንድ አውሮጳዊ እንዴት ኢትዮጵያ ውስጥ ከአስራ አራት አመት በላይ በየ አብነት ትምህርት ቤት እየተንከራተተ፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ ትምህርት ሊማር ይችላል?  በዘርአ ያዕቆብ ዘመን እኮ የነበሩት አውሮጳዊያን ኢትዮጵያን ለማሰልጠን፣ ከድንቁርና ለማውጣት የመጡ እንጅ ለኛ ባህላዊ እሴቶች ግድ የነበራቸው እኮ አልነበሩም፡፡ (ዛሬስ ግድ አላቸው እንዴ?)። እውነቱን ለመናገር የዘርአ ያዕቆብ አልባሳት አሊያም ወዙ ያረፈባቸው እቃዎች ተገኝተው፣ የዘረመል (DNA) ምርመራ ተደርጎ አውሮጳዊነቱ ቢረጋገጥ እንኳን ቅዱስ ጊዮርጊስን አሊያም አቡየ ጻዲቁን ኢትዮጵያዊ ያደረግናቸውን ያህል እርሱም ኢትዮጵያዊ ከመሆን አያመልጥም።
እንደው ነገሩን ለማነሳሳት ያህል እነዚህን ጉዳዮችን አነሳኋቸው እንጅ ጠንካራ መሞገቻ ይሆኑኛል ብዬ ተመክቼባቸው አይደለም። አስፈላጊ ከሆነ ወደፊት የፍልስፍናው መልክ ኢትዮጵያዊ ስለመሆኑ መነጋገር ይቻላል። በእርግጥ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን “ዘርአ ያዕቆብ ያንስብናል፤ የኢትዮጵያን ፍልስፍና አይወክልም” የሚል ድንቅ መሞገቻ አላቸው እሰየው ነው። እነ ቅዱስ ያሬድን፣እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን፣ እነ ተዋኔን በደንብ አጥንተን የህዝብ መወያያ እስከምናደርጋቸው ድረስ ግን ዘርአ ያዕቆብን ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርልን።
የግዕዝ ጥቅሶች በሙሉ ከዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ መፅሐፍ የተወሰዱ ናቸው፡፡

Published in ህብረተሰብ

አቶ ግርማ እና የፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት ሁለተኛ ክስ ቀርቦባቸዋል
የተከሰስንበትን ጉዳይ በግል ጠበቃ ቀጥረን እየተከራከርን ነው
ግቢው ደን ስለሌለው እንጂ ከቤተመንግስት አይለይም
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ደሞዛቸው ስንት ነበር? ጡረታቸውስ?

የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ የ12 ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ተጠናቆ ከቤተመንግስት ሲወጡ፣የፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት ከተከራየላቸው መኖርያ ቤት ጋር በተገናኘ  ውዝግቦች የተፈጠሩ ሲሆን ሁለት ክሶችም ተመስርቶባቸዋል - በእሳቸውና በፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት ላይ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ወደ መኖርያ ቤታቸው ያመራሁትም በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ላነጋግራቸው አስቤ  ነው፡፡ በወር 400 ሺ ብር ገደማ ኪራይ የሚከፈልበት ባለ 3 ፎቅ መኖርያ ቤታቸው  በኃይሌ ገብረሥላሴ ጎዳና፣ ከአክሱም ሆቴል በስተጀርባ ነው፡፡
መኖርያ ቤታቸው በር ላይ ስደርስ የተቀበሉኝ የፌደራል ፖሊስ አባላት ነበሩ፡፡ ጉዳዬን አስረድቼ  ቀጠሮ መያዜ ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ቅጥር ግቢው እንድዘልቅ ተፈቀደልኝ፡፡ በስተግራ በኩል ቀልብ በሚማርከው መናፈሻ ላይ ዓይኖቼን እያንከራተትኩ ነበር ወደ ዋናው መኖርያ ቤት መግቢያ በር ያመራሁት፡፡
ኮሪደሩ በቀጥታ ወደ እንግዳ መቀበያውና የመመገቢያ ክፍሉ ያደርሳል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የአቶ ግርማን ልጅ መናንና በጥናት ላይ የነበሩ ሁለት ልጆቿን አገኘን፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላም ምቾት በሚሰጥና በሚደላ የቆዳ ሶፋ ላይ አረፍ እንድንል ተጋበዝን፡፡ ቀና ስል ግድግዳው ላይ ትልቅ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን ተሰቅሎ  ተመለከትኩ፡፡ ዓይኖቼ ቀጥሎ ያነጣጠሩት በቀድሞው ፕሬዚዳንት  ግርማ ወ/ጊዮርጊስና ቤተሰቦቻቸው ፎቶግራፎች ላይ ነበር፡፡ ፎቶዎቹም ግድግዳው ላይ ነው የተሰቀሉት፡፡ ለጥቂት ደቂቃ ከተቀመጥኩ በኋላ ከሚደላው ሶፋ ላይ ለመነሳት ተገደድኩ፡፡ ሜሮን በተባለችው  የመኖርያ ቤቱ አስተናጋጅ አማካኝነት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢሮ ወደሚገኝበት ሁለተኛ ፎቅ ለመሄድ፣ የዳን ቴክኖ ክራፍት ሥሪት በሆነው አሳንሰር (ሊፍት) ውስጥ ገባን፡፡ አሳንሰሩ ከ1ኛ ፎቅ እስከ 3ኛ ፎቅ ድረስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡  
  ገና ወደ ቢሮው እንደዘለቅሁ ዓይኔ ያረፈው ጠረጴዛው ላይ ወዳሉት የወረቀቶች ክምር ነበር፡፡ “አቶ ግርማ አሁንም ይሰራሉ ማለት ነው?” - ስል ራሴን ጠየቅሁኝ፡፡ በዊል ቼር ላይ የተቀመጡት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ትንሽዬ ሬድዮ ከፍተው እያዳመጡ ነበር፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ለጥቂት ደቂቃዎች ዓይን መግለጫ ወግ ስናወጋ ቆየንና ወደ ቁምነገራችን ገባን፡፡ መቅረፀ ድምፄን አውጥቼ ቃለመጠይቁን ጀመርኩ፡፡
ከ12 ዓመታት የቤተመንግስት ኑሮ በኋላ በግለሰብ የኪራይ ቤት ውስጥ መኖር ምን ይመስላል?እንዴት ነው  ቤቱ ተስማማዎት?
በጣም ደስ የሚል ቦታ ነው፤ደን ስለሌለው ነው እንጂ ከቤተመንግስት አይለይም፡፡ ቤተመንግስት በደን የተሞላ ነው፡፡
በዚህ ቤትና ቀድመው ሊከራዩት በነበረው ቤት ዙሪያ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የዘለቁ  ውዝግቦች ተፈጥረዋል፡፡  የውዝግቦቹ መንስኤ ምንድነው ?
እኔ እዚህ ውዝግቡ ውስጥ የለሁበትም፡፡ ማን እንደተከራየውና እንዴት እንደተከራዩት አላውቅም።  የሆኖ ሆኖ የፅ/ቤቱ ሃላፊ ትመስለኛለች፡፡  መጀመሪያ የተከራየችው  ቤት የሚመቸን አልሆነም፤ ቤተሰቦቼም  ይሄኛውን መረጡ፡፡ በዚህ ስንስማማ የበፊቱን  ውል አቋርጠው እዚህ ገባን፡፡ በዚህ የተነሳ  ነው ውዝግቡ የተፈጠረው፡፡
ውዝግቦቹ  ፍርድ ቤት ከመድረሳቸው በፊት እርስዎ መፍትሄ ለማበጀት አልሞከሩም?
ይሄ የአስተዳደር ጉዳይ ስለሆነና  የፅ/ቤቱን  ሃላፊን ስለሚመለከት፤ እዛ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ገብቼ ይህንን አድርጉ፣ ይህንን አታድርጉ አላልኩም።
የፕሬዚዳንት ፅ/ቤቱ ቤቱን ሲከራይ ያውቁ ነበር?
ቤት ሲፈልጉ እንደነበርና እንደምንከራይም አውቃለሁ፡፡ እንደውም ከፈረንሳይ በላይ እንጦጦ አካባቢ ተገኝቶ ነበር፤ ይሄኛው ቤት ሶስተኛ ነው፡፡ ልጄ ይሄን አይታው ይሻላል ብላ ተመረጠ፡፡
እርስዎስ --- መርጠውት ነበር?
እኔ እንደውም አዲስ አበባ የመኖር ሃሳብ አልነበረኝም፤ አገሬ እኖራለሁ ብዬ ነበረ፡፡
ከሥልጣን የተሰናበቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች መኖሪያ ቤትን  በተመለከተ ህጉ ከአራት እስከ አምስት መኝታ ክፍሎች ያሉት በማለት ያስቀምጣል፤ ይሄ ቤት ግን ከሃያ በላይ ክፍሎች አሉት፡፡ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
ህጉ ይሄንን ያህል ክፍል ይከራያል የሚል አይመስለኝም፤እንደሚበቃው መጠን ነው የሚለው፤ ቤተሰቤ ሃያ ቢሆን የሚበቃኝ ሃያ ክፍል ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ገደብ ያለው ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ እኛ በዚህ ቤት ውስጥ ሰራተኞችን ጨምሮ ከአስር በላይ ሆነን ነው የምንኖረው፡፡
ይሄን ቤት ያከራየው የኮሚሽን ሠራተኛ የአገልግሎት ክፍያ አልተከፈለኝም በሚል ክስ ሲመሰርት፣ የፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት የጠበቃ ባለሙያ የለኝም በሚል ፍትህ ሚኒስቴር ወክሎ እንዲከራከርለት  ጠይቋል፡፡ እርስዎ ፕሬዚዳንት ሳሉም ፅ/ቤቱ የህግ ባለሙያ አልነበረውም ማለት ነው?
ይህን ያወቅሁት አሁን ነው፡፡ በፊት ጠበቃ የሚያስፈልገው ነገር ነበር ወይ? አላውቅም። ለቤቱ  ጉዳይ ጠበቃ የሚያሳፈልገው ከሆነም ለእለቱ የሚሆን አንድ ጠበቃ መቅጠር የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ የሆነ ሆኖ መንግስት ሲከሰስ የሚመልስበት መንገድ ስላለው ሊሆን ይችላል ወደ ፍትህ ሚኒስቴር የላከው፡፡ ቤቱን ካገናኘን የኮሚሽን ሰራተኛ ጋር የተዋዋለችው ልጄ ናት። ክሱም ለእኛ በግል ስለሆነና  ፅ/ቤቱ አይወክልም ስለተባልን፣በግላችን ጠበቃ ቀጥረን እየተከራከርን ነው፤ፍርድ ቤቱም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት አብዛኛው ስራ ከህግ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንዴት የህግ ባለሙያ የለውም?
አዋጅ ማፅደቅ፣ ለታራሚ ምህረት መስጠት ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎች ነበሩ፤ ጠበቆች ግን አይደሉም፡፡
በሥልጣን ዘመንዎ በየአመቱ ስንት እስረኞች ምህረት ይደረግላቸው ነበር?
 ምህረት እንደጠየቁትና ይገባቸዋል እንደተባሉት አይነት ነው፤ አምስት ሺህ ስድስት ሺህ ይደርሳሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ሳሉ ደሞዝዎ ስንት ነበር? አሁንስ ጡረታዎ?
ደሞዜን መናገር አስፈላጊ ከሆነ ዘጠኝ ሺህ ብር ነበር፤ አሁንም አልተቀነሰም፡፡
ከፕሬዚዳንትነት ከለቀቁ በኋላ ምን እየሰሩ ነው?
አሁን ምንም የምሰራው የመንግስት ስራ የለም። በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ቼር ኢትዮጵያ ከሚባል በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር ሽምጥ ሸለቆ ውስጥ የጠፉትን ደኖች መልሶ ለማልማት እየተጋን ነው፡፡
አሜሪካ ውስጥ ፕሬዚዳንቶች ከስልጣን ከወረዱም በኋላ በፕሬዚዳንትነት ስያሜያቸው ነው የሚጠሩት፡፡ ፕሬዚዳንት ክሊንተን --- ፕሬዚዳንት ቡሽ -- እየተባሉ፡፡ እርስዎስ?
ያው ነው፤ እኔ “የቀድሞው” የሚለውን ጨምሬበታለሁ እንጂ፡፡
ከወዳጅ ዘመድዎ ጋር ያለዎት ግንኙነት ቤተመንግስት በነበሩ ጊዜና አሁን ምን ይመስላል?
ምንም ልዩነት የለውም፤ ዘመድ ወዳጅ የሆነ በፊትም አለ፤አሁንም አለ፡፡
በስልጣን ላይ ሳሉ ቁጭ ብድግ ሲል ከርሞ፣ ከወረዱ በኋላ ፊቱን ያዞረና የታዘቡት ሰው አለ?
እንዲህ አይነት ሰው እኔ ጋ መጥቶ አያውቅም፣ድሮ የሚመጣ አሁንም ይመጣል፡፡ የሚጠይቁኝን እኔ ማድረግ ከቻልኩ አደርጋለሁ፤ ካልቻልኩ ደግሞ ለሚችል ሰው እንዲያደርጉላቸው እነግራለሁ፡፡
ቃለመጠይቁን እንዳጠናቀቅሁ መኖርያ ቤታቸውን መጎብኘት እችል እንደሆነ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ጠየቅኋቸው፡፡ እሳቸውም “በደስታ” አሉና ወደ ቢሮአቸው ያመጣችኝን ሜሮንን  መደቡልኝ፡፡  ከሜሮን ጋር ጉብኝቴን ጀመርኩ - ከምድር ቤት፡፡
በምድር ቤቱ  ስድስት የሰራተኞች ማደሪያ ክፍሎች፣ አንድ ጌጣጌጦችና ፎቶዎችን የያዘ ሰፊ ክፍል፣ አንድ በዘመናዊ የስፖርት መሳሪያዎች የተደራጀ ጂም፣ አንድ ስቲም ባዝና የምግብ ማብሰያ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡
ከዋናው የመኖርያ ቤቱ ህንፃ  በስተኋላ ስድስት የፌደራል ፖሊስ አባላት የማረፊያ ክፍሎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ክፍሎች ትይዩ ደግሞ ትልቅ የመዋኛ ገንዳ ይገኛል፡፡
በውጪ በኩል የሚያስወጣውን ደረጃ ይዘን ወደ አንደኛ ፎቅ ወጣን፡፡ በዚህ ፎቅ ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መኝታ ክፍልና የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች ናቸው ያሉት፡፡ ወደ ሁለተኛ ፎቅ ወጣን- የፕሬዚዳንቱ ቢሮ ያለበት ማለት ነው፡፡ ከቢሮው ሌላ የአቶ ግርማ ልጆችና ባለቤታቸው መኝታ ክፍሎች እንዲሁም የእንግዶች ማረፊያን ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ክፍሎች ይዟል፡፡
በመጨረሻም የቤቱ አናት (ቴራስ) ላይ ወጣን። አዲስ አበባ ቁልጭ ብላ ነው የምትታየው፡፡ ዘመናዊ ባር የተዘጋጀለት ቴራሱ፤ ለትላልቅ ድግሶችና ፕሮግራሞች የሚሆን ዘና ያለ ቦታ  አለው፡፡
የአቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ መኖርያ ቤትን የሚጠብቁ እዚያው ነዋሪ የሆኑ አምስት የፌደራል ፖሊስ አባላት ያሉ ሲሆን ስድስት ተመላላሽና ቋሚ የፅዳትና የምግብ ዝግጅት ሰራተኞችም እንዳሉ ከሜሮን ማብራርያ ለመረዳት ችያለሁ። ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን በመላላክ የምታገለግል አንዲት ሠራተኛም አለች፡፡ ከእነአጃቢያቸው ጭምር አራት መኪኖችም ተመድቦላቸዋል - የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፡፡

Saturday, 15 February 2014 12:41

ወስላታው ግብር ከፋይ!

“ክቡር ፍርድ ቤት፤ መስረቄ እውነት ነው፣ግን ግብር ከፋይ ነኝ”

በየትም አገር ያለ መንግሥት በባህርዩም ሆነ በተቋቋመበት ሕግና ሥርዓት ወይም ርዕዮተ ዓለም ሊለያይ ቢችልም በአስገባሪነቱ ግን አንድ ነው፡፡ መንግሥት ሆኖ ብቅ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ከሚገዛው ወይም ከሚያስተዳድረው ወይም ከሚመራው ህዝብ ላይ ግብር የመሰብሰብ መብት አለው። ይህ “ተፈጥሮአዊ” መብቱ ነው ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም የማንኛውም አገር መንግሥት ከአገሩ ህዝብ ላይ ግብር መሰብሰብ ካልቻለ ህልውና የለውም፡፡ መንግሥት የሌለው አገርና ህዝብ ደግሞ እንደ ዝንጀሮ መንጋ ጉልበተኞች የሚገዙት፤ ወደፈለጉበት የጥፋት ጐዳና የሚመሩትና ራሱም ለጥፋት የተዘጋጀ ይሆናል፡፡
 መንግሥት ግብር የመሰብሰብ መብቱ ተፈጥሮአዊ  ነው ቢባልም የግብሩን መጠንና ዓይነት ግን በህግ መወሰን ይኖርበታል፡፡ በዚያው ልክ ስልሞውን አንቆ ግብር የሚቀበለውን (በግዱ የሚያስከፍለውን) ህዝብ ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፣ ይህን ካላደረገ ወድዶና ፈቅዶ የመረጠው ህዝብ ወይም እንደ መንግስቱ ባህርይ በግድ የሚገዛና የአምባገነኖች ሰለባ የሆነውም ቢሆን የሰላሙ መደፍረስ፣ የኑሮው ቀውስ እየተባባሰ ሲመጣ፣ወደ አጠቃላይ ትርምስ ያመራና አምባገነኖችም አገሪቱም አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡
ምንም እንኳ ለህዝብ ሰላምና ፀጥታ ሲባል የሚቋቋሙ የፖሊስ፣ የፀጥታ ኃይልና የፍትህ አካላት መሣሪያነታቸው ለገዥ መደቦች እየሆነ አመርቂ ሥራ ማከናወን ቢሳናቸውም፣ በአገራት ሁሉ የመቋቋማቸው ዓላማ ህዝብን ያማከለ ነው፡፡ ግን የሚሾም የሚሽራቸው፣ የሚገነባ የሚያፈርሳቸው መንግሥት ስለሆነ ነገራቸው ሁሉ “እንደንጉሡ አጐንብሱ” ሆኖ ቀርቷል፡፡
በዓለም ላይ ካሉ አገሮች ሁሉ ከፍተኛ ግብር በመጣልና በመሰብሰብ የሚታወቁት የስካንዲቪያን አገሮች ናቸው፤ ሕግና ሥርዓት በማስጠበቅ በኩልም የሚወዳደራቸው የለም፡፡ ቀላል ማሳያ ልጥቀስ፤ አንድ ወቅት ስዊድንን የመጐብኘት ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር። በእግር ስንዘዋወር ያስተዋልሁት ጉዳይ መቸም የሚረሳኝ አይደለም፤ ከእኔ ጋር የነበሩ ያገሬ ሰዎችና አስጐብኛችን መንገድ ለማቋረጥ ገና ጫፉ ስንደርስ መኪኖች ሁሉ በርቀት ይቆማሉ፡፡ ጉዳዩ ሲደጋገም አሽከርካሪዎች ለምን እንዲህ እንደሚያደርጉ አስጐብኝያችንን ጠየቅኋት፤ የሰጠችኝ መልስ እጅግ አስገራሚ ነበር፡፡
“በሀገራችሁ ቅድሚያ የሚሰጠው ለእግረኛ ነው ለአሽከርካሪ?” ብላ መልሳ ጠየቀችኝ
“ዜብራ መንገድ ላይ ገና መች ደረስንና?” አልኋት የምንተፍረቴን፤ አገሬ በሰው አገር ሰው እንዳትታማብኝ በመጠንቀቅ፡፡
“ፖሊስም በአካባቢው አይታይም፤ ቅድሚያ ባይሰጡስ ማን ይቆጣጠራቸዋል?” የሚል ሌላ ጥያቄ አከልሁላት፡፡
“ፖሊስ? ፖሊስ መንገድ ላይ ምን ሊሠራ ይቆማል? እኛ አገርኮ መንገዶች ሁሉ በካሜራ የተደራጀ የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት ተዘርግቶላቸዋል፤ ፖሊሶች ጣቢያቸው ውስጥ ከሚገኙ ቢሮዎቻቸው ቁጭ ብለው በየትኛው መንገድ ላይ ምን እንደተፈጠረ፣ ማን ችግሩን እንዳደረሰ መከታተል ይችላሉ፡፡ በአጥፊው ግለሰብ ላይ ተገቢውን ቅጣት ይጥሉና፣ ከባንክ ሂሳቡ የቅጣቱ ገንዘብ ተቆርጦ ደረሰኙ በአድራሻው ይላክለታል እንጂ ከአጥፊው ጋር ሲጨቃጨቁ የሚውሉበት ምንም ምክንያት የለም፤ ፖሊስ የሚያስፈልገው ምን አልባት ከባድ ወንጀል ከተፈፀመ ብቻ ነው፡፡ እሱም ቢሆን የሚያጋጥምበት ጊዜ በጣም ጥቂት ነው” አለችኝ፡፡
በእውነት ቀናሁ፤ ካየሁት የመንገድ ጽዳት፣ የቤት አሠራር ውበትና የህዝቡ ዕድገት ይልቅ በዚህኛው ሥርዓታቸው ከልብ ቀናሁ፡፡ ምን አለ የእኛ አገር የትራፊክ ፖሊሶችን ፊት የማያሳይ ሥርዓት ቢዘረጋና አሽከርካሪዎች እንደ ስዊድን ለሰው ፊት ሳይሆን ለህግ ብቻ ተገዥ ሆነው፣ በየቀኑ የንፁሃን ደም አስፋልት ሲያጥብ ከማየት በተገላገልን አልኩ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ምኞት ነው፡፡
እዚያው ስዊድን ውስጥ አንድ ችሎት ላይ የሰማሁት ጉዳይም አስገርሞኛል፤ አንድ ግለሰብ እኩለ ሌሊት ላይ በከተማዋ ሲዘዋወር አንድ የማያውቀው ሰው ያስፈራራዋል፤ ግን የደረሰበት አንዳችም ጉዳት የለም፡፡ ሰውየው ምን አደረገ መሰላችሁ? ጠዋት ላይ “ግብር የምከፍልህኮ መብቴን በተሟላ መልኩ ልታስከብርልኝ ነው፤ አንተ ግን ከስጋት ነፃ የመሆን መብቴን አላስከበርክልኝም” ብሎ በመንግሥት ላይ ክስ መሠረተ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት እሰጥ አገባ ሊል አይችልም፤ ዜጐቹን ከሁሉም በላይ ያምናል፣ የዜጐቹን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣት እንዳለበትም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ስለዚህ የዜጋውን ከ “ስጋት ነፃ የመሆን መብትን” ለመጠበቅ ሲባል ካሳ ከፈለና ተገላገለ፡፡ እኛ አገርኮ እንኳን ከስጋት ነፃ የመሆን መብት--- ብቻ ሆድ ይፍጀው፡፡
ግብር እንከፍላለን፤ በተቀጣሪነት ከምናገኘው አነስተኛ ገቢ እንገብራለን፤ ከምንጠጣው ሻይና ከምንበላው ምግብ ሳይቀር ግብር ይቆረጥብናል፡፡ ግን ሰላማችን የታለ? ገዢያችንኮ ብዙ ነው፤ የመንደር ዱርዬው፣ የታክሲ ወያላው፣ ወረፋ አስከባሪው፣ ወረዳው፣ ቀበሌው፣ ክፍለ ከተማው፣ ከተማ አስተዳደሩ፣ ምኑ ቅጡ…የገዢያችን ቁጥር መብዛቱ፤ ግን መብታችንን የሚያስከብርልን አካል የቱ እንደ ሆነ በውል አይታወቅም፡፡
ርዕሰ ጉዳያችን ከግብር ጋር የተያያዘ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ በሃገራችን የተጨማሪ ዕሴት ታክስ አዋጅ ከወጣ በኋላ በርካታ ሰዎች ለእስራትና ለስደት ተዳርገዋል፤ አንዳንዶች በጥፋታቸው ሌሎች ደግሞ ከግብር ሰብሳቢው ተቋም አንዳንድ ወስላታ ሰራተኞችና ኃላፊዎች ጋር መሞዳሞድ አቅቷቸው፡፡
የተጨማሪ ዕሴት ታክሱ የመንግሥትን ገቢ ከማሳደግ አንፃር ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አያከራክርም፤ የመንግሥት ገቢ ሲያድግ የሃገሪቱ የመሠረተ ልማት አውታሮች ሊስፋፉ እንደሚችሉም እሙን ነው፡፡ ግን በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ይህ እየሆነ አይመስለኝም፤ የመብራት፣ የስልክ፣ የውሃና የፍትህ አገልግሎት እያደር እየዘቀጠ ነው፡፡ በአንፃሩ ወስላታ ባለሥልጣናትና የቆረጣ ነጋዴዎች ከመንግሥት በላይ እያደጉ መሆናቸውን በራሱ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በኩል እየሰማን ነው፡፡
የስድስት ዓመት የመንግሥት ሥራ አገልግሎት ብቻ ያለው ጐረምሳ፣ የሰላሳ አምስት ሚሊዮን ብር ባለቤት ሲሆን “ያንተ ያለህ! እግዚኦ ሰውረን!” ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊባል እንደሚችል አይገባኝም፡፡ ይህ’ኮ ማሳያ ነው፤ አንድ የቅርንጫፍ ሠራተኛ ያውም ለከፍተኛ ኃላፊነት ያልበቃ ይህን ያህል ገንዘብ መዝረፍ ከቻለ የእሱ የበላዮችስ? አሁንም ሆድ ይፍጀው ነው፡፡
ሙስና አሁን የተፈጠረ አስደንጋጭ ክስተት ነው ባይባልም የተጨማሪ ዕሴት ታክስ አዋጁ ከወጣ በኋላ  ብዙ አስደንጋጭ ጉዳዮችን እየሰማን ነው። በአራጣ አበዳሪነት ወንጀል ተከሰው፣ ያልተፈቀደ ንግድ በማካሄድ ወንጀል ተፈርዶባቸው፣ ሻይ ሲሸጡ የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ደረሰኝ ባለመስጠት ተይዘው … በርካታ ሰዎች ከርቸሌ ወርደዋል፡፡
ሰሞኑን በአንድ የወንጀል ችሎት ያየሁት ተከሳሽ ግን እጅግ አስገርሞኛል፡፡ የሰላሳ ዓመት ጐልማሳ ሲሆን ተወልዶ ያደገው ሽሮሜዳ አካባቢ ነው፡፡ ችሎት የቀረበው በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ መሆኑን ከክስ መዝገቡ ላይ ዳኛው ሲያነቡ ሰምቻለሁ፡፡ ዳኛው የክሱን ዝርዝር ጉዳይ ካነበቡለት በኋላ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ ጠየቁት፡፡ ተከሳሹ ምንም ዓይነት የመደናገጥም ሆነ የፍርሃት ምልክት ሳያሳይ “አዎ ሰርቄያለሁ” አለ፡፡ ለምን እንደሰረቀ ማስረዳት ሲጀምር፣ የዳኛውም ሆነ የችሎት ታዳሚዎች ጆሮ እንደ ቀስት ተቀሰረ
 “ክቡር ፍርድ ቤት! መስረቄ እውነት ነው፤ ግን ግብር ከፋይ ነኝ”
“ምን?” ዳኛው አንገታቸውን ወደ ተከሳሹ አስግገው ጠየቁት፡፡
 “አንድ ኪዮስክ ነበረችኝ፤ ለተወሰነ ጊዜ ደህና እሰራባት ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ከሰርሁና ምንም መላወሻ አጣሁ፡፡ መንግሥት ደሞ ግብር አምጣ ብሎ ያዘኝ። የእናቴን ቤት ከማሸጥባት ብዬ ወደ ስርቆት ገባሁ፤ ግን’ኮ የተከበሩ ዳኛ! ምንም ነገር ብሰርቅ ለመንግሥት መገበሬን አላቋርጥም”
“ከሰረቅኸው ላይ?” ዳኛው ጣልቃ ገብተው ጠየቁት፡፡
“አዎ…! ምንም ነገር ብሰርቅ እገብራለሁ፤ ሌላው ቢቀር ሞባይል ነጥቄ እንኳ ከማገኘው ሽያጭ ላይ ለመንግሥት መገበሬን አላቆምም”
“ለምን?” ዳኛው እንደ ገና ጠየቁት፡፡
“ሥራ ነዋ ክቡር ዳኛ! ደሞም ስሰርቅ የምሸማቀቀውን ያህል፤ ለመንግሥት ግብር ሳስገባ ዕዳዬ ሁሉ የቀለለኝ መስሎ ይሰማኛል”
ብዙዎቻችን ሳቃችንን መቆጣጠር ባለመቻላችን ችሎቱን ትተን ወጣን፡፡ ሆኖም ከሌባው የምንማራቸው ሁለት ነገሮች ያሉ ይመስለኛል። በአንድ በኩል ህግን እየጣሰ፣ በሌላ በኩል ለግብር ያለው ከበሬታና ጥንቃቄ የግለሰቡን ልዩ ባህርይ ያመለክታል፡፡
ግብርን በታማኝነት መክፈልን ከወስላታው ግብር ከፋይ ስንማር፤ ሌብነትን የችግሮች ሁሉ መፍትሄ አድርጎ መውሰድ ከተጠያቂነት እንደማያድን ደግሞ ከህጉና ከፍርድ መማር ይቻላል። ለማንኛውም ግብር ከፋዩን ወስላታ “ልማታዊው ሌባ” ብዬ አምቼዋለሁ፡፡

Saturday, 15 February 2014 12:41

ገሀድ-ዘለል ግጥም)


ነብስ-ያወቀ ውሻና ነብስ-ያላወቀ ሰው

ከዕለታት አንድ ቀን፤ ነብስ-ያወቀ ውሻ፣ አንዲት መሸታ ቤት፣ ግሮሠሪ ገብቶ፤  
ነብስ-ያላወቀ ሰው፣ ሲመሽት አግኝቶ
እንደ ሰዉ “ሃይ ሃይ!፣ “ፒስ ነው” “ኩል ነው!” - ሳይል፤
በወግ እጅ ነስቶ እንዳገሩ ባህል፣
ሰላምታውን ሰጥቶ፣ በውሻ ትህትና
ጂን አዞ ቁጭ አለ-በረዶና ሎሚ፣ ባናቱ አረገና፡፡
ሰውዬው አንድ እግሩን፣ በሌላ ወንበር ላይ፣ አሻግሮ ቸክሎ
በዚህኛው ጐኑ፤ ባለጌ ወንበር ላይ፣ ባለጌ እግሩን ሰቅሎ
ቡችላ ቀለበት፣ የእጅ-አምባር ሠንሠለት…፣ በክፍት ሸሚዙ የሚታይ ሀብል ወረት
እንዲያው በጥቅሉ፣ መስሎ ሱቅ ወርቅ ቤት ..
በእጁ እሚሽከረከር፣ መኪና-ቁልፍ ዓይነት … ደሞ ጨምሮበት
ይዞ ኮራ ብሎ፣ ብልጭልጭ ሱፍ ለብሷል … በጅንን-ዕይታ፤ ውሻውን ያየዋል፡፡
ውሻ ጂን ሲጠጣ፣ አይቶ አያውቅምና በቅጡ ገርሞታል!!
ውሻውን ሊጠይቅ ገና ዐይኑን ሲያቀና
“ምነው ተገርመሀል? ግር ያለህ መስለሀል?” አለው ውሻው
ቀድሞ፤  
“ውሻ ግሮሠሪ ገብቶ ሲጠጣ ሳይ … እንዴት አልገረም?” አለ ሰው
ተደሞ፤  
ውሻ በውሻኛ ፈገግ-ለቀቅ ብሎ፣ … ድምፁንም፣ ጂኑንም፤ በውል አጣጥሞ
“ከብዙ ግብዝ ሰው፣ ቅን ውሻ እንደሚሻል፣ ሳይህ ነው
የገባኝ
በድህነትህ ላይ፤ በአንጐልክም፣ በሰውህም-መዘነጥህ
ገርሞኝ
ማንኛውም ፍጡር፣ ከአካላቱ ይልቅ፣ ጌጣ-ጌጡ በዝቶ፣
የበቅሎ መጣምር፣ ግላስ ሲመስልብኝ
ሰው የጌጥ ዕቃ ነው
ስንጥቅጥቅ መስተዋት
ቁሳቁስ ነው አልኩኝ!”
ሰውዬው ገረመው፤
“እንዲህ ልትል የቻልክ፣ እንዴት ብታየኝ ነው?” አለና ጠየቀው
“እኔማ ያየሁህ፣ በውሻ አተያይ ነው፡፡
ቆይ አንዴ ታገሠኝ፣ ከአፍታ በኋላ ደግሞ እንገናኛ
አለው በሬዲዮው በ “ኤፍ-ኤም”ኛ!!”
መናገር ሊቀጥል ውሻ በውሻኛ
ጂኑን ጠጣ ጠጣ … አፍ-አፉን ላስ ላስ …
የዝናብ መጥረጊያ እንዳለው መኪና ግራ ቀኙን ዳሰስ
ሊፕስቲክ አውጥቶ ከንፈሩን ተም-ተም፣ ላይ-ታቹን ላግ-ላግ፣ እንደ ሴት-ቄንጠኛ …
“ሰዎች ስትባሉ፣ እሩጫ አበዛችሁ
እኛንም ጨምሯል፣ አጉል ህይወታችሁ …
እኔም እንደናንተ፣ እንዳቅሜ ሮጣለሁ
ትንሽ እጠጣና፣ ፀጉር ቤት እሄዳለሁ
ፀጉሬን አሳጥሬ፣ እስተካከላለሁ
ብታምንም ባታምንም፣ ቀለም መቀባባት … ሂውማን ሄይር
ምናምን … በጣም እጠላለሁ፡፡
ከዛ ሠርግ አለብኝ፣ ከመንጋ አጃቢ ጋር፣ ገና እጃጃላለሁ፡፡  
አበሻ ሲገበዝ፣ ላንድ ቀን ሲሞሸር፣ በምፀት አያለሁ፡፡
የነገ ፍቺውን፣ ዛሬ ሲያመቻቸው፣ እታዘበዋለሁ!
የውሰት ቬሎውን፣ የውሰት ጌጥ-ወርቁን፣ የውሰት
ደስታውን
… ሽንጣም ሊመዚኑን … ሲመዝን አያለሁ!!  
ሰውዬው በግርምት እንዲህ ሲል ጠየቀ፡-
“አንተ ለመሆኑ የፈረንጅ ውሻ ነህ፤ የአበሻ ውሻ ነህ?”
“ማይ ጋድ!” አለ ውሻ፣ “በተማረ” ልሣን፣ በፃድቅ ውሻኛ፡፡
“ውሾች እንደ እናንተ እንደ ነጭ-አምልኮች “ፈረንጅ”
“አበሽ”
ብለው፤ ውሻን አይፈርጁም፤ አንዱን ዘር ከሌላው
አያበላልጡም፡፡  
ይልቅ ልጠይቅህ፣ አንድ ተረት መሳይ፣ አላችሁ አባባል
“ውሾን ያነሳ ሰው ውሾን ይሁን” የሚል
ይህ እንዴት ተባለ፣ ከየት መጣ እሄ ቃል?”

ሰውዬው መለሰ፤
“ከዕለታት አንድ ቀን፣ ርሀብ የመታቸው፣ አንድ ልጅና አባት
ማሣቸው ሲቃጠል በድንገተኛ እሳት፡፡
አይተው እንደልማድ፤ ለማምለጥ ያልቻለ አንድ ውሻ አብሮ ሲነድ፤
“ተጠብሷል! እንብላው! ምን ይለናል?” ብለው
ከጠኔ ሊድኑ በሉት ተስገብግበው፡፡  
ግን እንስማማ አሉ
ለማንም ላይነግሩ በውል ተማማሉ፡-
ውሾን ያነሳ ሰው፣ ውሾን ይሁን አሉ”፡፡
ውሻው እየጠጣ፣ ከት ከት ብሎ ጮኸ፤ ሳቀ፣ በውሻኛ
“ሰዎች ስትባሉ፣ አያልቅም ጉዳችሁ …
ከበላችሁ ወዲያ፣ ህግ ማውጣትማ፣ ታቁበታላችሁ!!
ለነውር ሥራችሁ፣ ለመሶቡ ግጣም፣ ታበጃጃላችሁ!
የሰው ልጅ ይሄው ነው፣
ውሻን ቅርጥፍ አርጐ ከበላ በኋላ
ውሾን ያነሳ ሰው ውሾን ይሁን የሚል ያመጣል መሀላ”
አለ ውሻ ሆዬ፣ ጂኑን አወራርዶ፤ ምፀት ማስታገሻ፤
“ሌላም ልጠይቅህ-‘ውሻ ምን አገባት፣ የምትገባው እርሻ’
የሚልም አላችሁ፣ ትርጉሙ ምንድነው፣ የቃሉ መነሻ?”
“ይሄ እንኳ ዘይቤ ነው - ሰው አለ ጉዳዩ ገብቶ ሲዘባርቅ
ወይም አለሙያው፣ በማያውቀው ጦር ውስጥ፣ ላይተኩስ ሲባርቅ
ወይም አላገሩ፣ አለወንዙ ገብቶ፣ አጉል ሲምቦጫረቅ
ይህ ተረት ይወሳል፣ ልኩን ለማሳወቅ!”
….
ከት ከት ብሎ ሳቀ፣ ውሻው ሞቅ እያለው
“ቅኔውና ኅብሩ፤ ስላቁ እዚህ ጋ ነው -
ገቢሩ የሰው ነው፣ ምሳሌው ውሻ ነው
ሰው አይረባም ያልኩህ፣ ይሄን ጨምሬ ነው!”
“ና ድገመኝ!” አለ፣ አሳለፊ ጠራ፤
በቅን ውሻነቱ፣ ጨምቶ እየኮራ!!
“ደሞም እንደውሻ ጭራህን አትቁላ” ሲሉ ሰምቻለሁ
“የእኛኑ ጭራ ነው፤ ሌላ ጭራ አላችሁ?!”
ሰውዬው ከቢራው ጥቂት ተጐንጭቶ
(ያው ጭራ እንደመቁላት ጥቂት ተወራጭቶ)
“ጭራ ወይም ጅራት፣ መንፈስ ነው፣ ምላስ ነው
የሐሞተ-ቢስ ሁሉ፣ የዥዋዥዌ ክር፣ የእጅ-መንሻ ድርድር
የአድር-ባይ፣ ቅቤ አንጓች፣ ተብትቦ ያሠረው! ቱሻ ወፍቾ ነው -”… አለና ነገረው፡፡  
“አይ የሰው ልጅ ማለት፣ ይገርመኛል ከቶ
ጭራውን ይቆላል፣ በውሻ አመካኝቶ!”
አለና ሎሚውን ጅኑ ውስጥ ጨማምቆ፣ ጨልጦ ተነሳ፡፡
ሰውዬው ቢራውን ጥቂት አጣጣመ
“አንድ ነገር ብቻ ልጠይቅህ እስቲ - ከመሄድህ በፊት፤
ዕውነት ውሻ ማነው?”
ውሻው በውሻኛ እንዲህ ሲል ፈፀመ፡-
“ውሻ ማነው አልከኝ? … ውውው ዋዋዋ! ዎዎዎ፣ ዋዋዋ!”
ብሎ በሆህኛ …  
“ውሻማ ራሴ ነኝ!!
እኔ ሞትኩ የምለው
የሰው ልጅ ለመሆን የሞከርኩ እለት ነው!
ለምን አትለኝም?
አየህ እዚህ እኛ አገር፣ ውሻና ሰው እኩል፣ ሲመሽት ቢገኝም
ሰውኮ እሚኖረው፣ በ “ሚስ-ኮል” ብቻ ነው፤
ሀብታሙ እሚኮራው፣ በባንክ ብድር ነው፤
አገሩ እሚሸልል፣ ባለም ባንክ ስፖንሰር፣ ነብሱን አሲዞ
ነው፤
ዜጋው አለሁ የሚል፣ ለየነብስ አባቱ፣ ኑዛዜ ሰጥቶ ነው፤  
ታዲያ እኔ ወዳጄ፤ ሰው ልሁን የምለው፣ ምን ልሁን ብዬ
ነው?!
አንተም የምትሞተው
ውሻ መሆን ላትችል፣ ውሻ ነኝ ካልክ ነው!
ቦታ አልቀይርህም!
ራስክን ችለህ ቁም-ማንነት የራስ ነው
(ራሳቸውን ለመሆን ላሰቡ) ታህሣሥ፤ 20006 ዓ.ም

Published in የግጥም ጥግ

በዓለም ላይ “የመርፊ ህግ” በመባል የሚታወቅ ህግ አለ፡፡ የምንሠራው ሥራ ሁሉ ስህተት ይሆናል ብሎ የማመን አዝማሚያ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የሚተረክ አንድ ተረት አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው፤ በአንድ በጣም በራበው ጠዋት፤ ቁርስ አስቀርቦ መብላት ጀመረ፡፡ ዳቦውን ሁለት ላይ ከፈለና አንዱን ግማሽ ቅቤ ቀባው፡፡ ጥሩ አድርጐ ግማሹን ክብ ዳር እስከዳር አሳምሮ ነው በቅቤው ያዳረሰው፡፡ ከዚያ ሻዩን ለማወራረጃ ስለሚፈልገው ስኳሩን አስቀድሞ ከቶ ሻዩን ብርጭቆው ውስጥ ቀድቶ እያዘጋጀ ሳለ፤ ሳያስበው ያን የተቀባ ግማሽ ዳቦ ከጠረጴዛው ገፋና ጣለው፡፡
ዳቦው ወለሉ ላይ ወደቀ፡፡
ደንግጦ ወደ ወለሉ ሲያይ በጣም አስገራሚ ነገር ገጠመው፡፡ የዳቦው ያልተቀባው ወገን ወደመሬት፤ የተቀባው ወገን ወደላይ መሆኑን አየ፡፡ አንዳች ተዓምር እንዳየ ሆኖ ተሰማው፡፡ ተደነቀ፡፡
ወደ ጓደኛዬ ሄደና፤
“ዛሬ ጉድ ነው ያየሁት!” አለ፡፡
“ምን አየህ?”
“ብታምኑም ባታምኑም - ተዓምር ነው ያየሁት!”
“እኮ ምን አየህ? ንገረና!?”
“ቁርስ ስበላ ድንገት ግማሹ ቅቤ የቀባሁት ዳቦ መሬት ወደቀ፡፡ የሚገርመው ያልተቀባው ወገን ወደታች የተቀባው ወደላይ ሆኖ ተገኘ!”
“እረ ባክህ? ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የተቀባ ዳቦ ሲወድቅኮ፤ ብዙ ጊዜ የተቀባው ወደ መሬት፣ ያልተቀባው ወደላይ ነው የሚሆነው፡፡ አንተ ያጋጠመህ ተዓምር ካልሆነ በስተቀር ወደላይ ሊሆን አይችልም። ምናልባት ለእኛ አልታወቀን ይሆናል እንጂ አንተ ቅዱስ ሳትሆን አትቀርም፡፡ አምላክ ምልክት ሲሰጥህ ነው” አለ
አንደኛው ጓደኛው፡፡
ከዚህ በኋላ በአንድ ጊዜ ወሬው በመንደሩ ተነዛ፡፡ ሁሉ ሰው ጆሮ ደረሰ፡፡
ሁሉ ሰው መጠያየቅ ጀመረ፡፡
“ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ? ማንም ሰው ያልተቀባው ወገን ወደታች ይሆናል ብሎ አይጠረጥርም፡፡ ዳቦው በተሳሳተ ወገንኮ ነው የወደቀው?” ተባለ፡፡
ማንም መልስ ሊሰጥበት ያልቻለ ትልቅ ጥያቄ ሆነ፡፡
በመጨረሻው “ለሰፈሩ ሊቅ ጥያቄውን እናቅርብለትና እሱ ይመልስልን” ተባለ፡፡
ወደመምህሩ ሊቅ ሄደው የሆነውን ተዓምር ነግረው እንዲያብራራላቸው ጠየቁት፡፡
አዋቂው፤ “በዚህ ጉዳይ ላይ፤ ለመፀለይ፣ ሃሳቡን ለማብላላትና መለኮታዊ ምጥቀት ለማግኘት፤ አንድ ማታ ያስፈልገኛል” አለ፡፡
ጊዜው ተሰጠው፡፡
በነጋታው በጉጉት ህዝቡ እየጠበቀው ሳለ መምህሩ መጥቶ፤
“ነገሩ እንኳን በጣም ቀላል ነው፡፡ ያ ዳቦ የወደቀው በትክክል መውደቅ ባለበት በኩል ነው፡፡ ቅቤው የተቀባው ግን በተሳሳተው ወገን ነው!!” አለ፡፡
                                                            *   *   *
እርግጥ በሀገራችን አንፃር ስናየው፤ ዳቦው ከሌለ ግማሹም ሆነ ሙሉው ተቀባ አልተቀባ ማለት አስቂኝ ይሆን ይሆናል፡፡ የተረቱ ምልኪ ግን፤ ስለወደቀውም ዳቦ አሉታዊ አስተሳሰብ ሊኖረን አይገባም ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ዳቦው የዳነው በተሳሳተ ወገን ስለተቀባ ነው የሚለው ሌላው አሉታዊ ምላሽ ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን። ህዝቡም መምህሩም አፍራሽ ይሆኑብናልና!
አንዳንዴ አንዳንድ ምናባዊ ፅንሰ-ሀሳብ ምድር ላይ ቢሆን ምናለበት ያሰኛል፡፡ የዳንቴ ፍልስፍና ለዚህ ይበጀናል፡፡
ሰይጣንን ከማግኘታችን በፊት የወንጀለኞች መቀጫ፤ አውቀው ኃጢአት የሰሩ የሚቃጠሉበት፤ ቦታ አንድ ህግ አለው ይባላል፡- የወሸሙና የከጀሉ፤ በዲያብሎስ ይገረፋሉ፡፡ ሸፋጮች አወናባጆች፣ አይነ ምድር ውስጥ ይደፈቃሉ አጨናባሪ አትራፊዎች እግር-ወደላይ-ራስ ወደ ታች ሆነው አዛባ ውስጥ ይዘፈቃሉ። ጠንቋዮች፣ ጠጠር ጣዮች፣ ዛጎል ወርዋሪዎች፤ አንገታቸው ወደ ጀርባ የሚዞርበት ምስል ይኖራቸዋል። አወናባጅ ፖለቲከኞች የአፈር-ውሃ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ይጣላሉ፡፡ አስመሳዮች መሸከም የማይችሉት ካፖርት ይጫንባቸዋል፡፡ ሌቦች በእባብ አለንጋ ይገረፋሉ፡፡ አጭበርባሪ የፖለቲካ አማካሪዎች በእሳት ይዋጣሉ የማይሆን ወሬ የሚነዙ ፍም ውስጥ ይቀበራሉ፣ ይለናል፡፡
ከዚህ ሁሉ ይሰውረን ዘንድ መንገዱን ያብጅልን! ይሄ የገባው እራሱን ይጠብቅ፡፡
የሃገራችን ውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ… የባንክ፣፣ የቀረጥ ወዘተ የማይነጣጠሉ ችግሮች፤ የዘንድሮ ጉዴስ እኔም ገረመኝ፡፡
አንዱን ስለው አንዱ አንዱ ባሰብኝ!
የሚለውን የዱሮ የኦርኬስትራ ኢትዮጵያን ዘፈን ያስታውሰናል፡፡ በዚያው ዘመን ስለ ሎተሪ አዟሪ በሚዘፈን ዜማ፤
“እስኪ ተመልከቱት፣ ይሄንን ፈሊጥ
እሱ እድል የሌለው፣ ዕድልን ሲሸጥ!” የሚልም ነበር፡፡ ከሁሉም ይሰውረን፡፡
ዛሬ “የባሰ አታምጣ!” ብሎ መፅናናትም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ እንደዕውነቱ ከሆነ የዕውቀትና የሙያ ክህሎታችን ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል ማለት እንጂ “ፓርቲዬ ከመደበኝ የትም ቦታ እሰራለሁ” ብቻውን መፍትሄ አያመጣም፡፡ ችግሩ የተፈጠረው በፓርቲ ምደባ ምክንያት ከሆነስ? ብሎ መጠየቅም ያባት ነው፡፡ ህዝባችን ፓርቲን እንዲያልም ሳይሆን አገር እንዲያልም ብናስብ መልካም ሳይሆን አይቀርም፡፡
የሀገራችን አካሄድ ዕውን፣ በዳቦ የተሳሳተ ወገን መቀባት? ቅቤውን አፈር አይነካውም በማለት? ዓበው እንደሚሉት ከተምኔታዊ (utopian) ገጠመኝ ይልቅ ሌላውን ግማሽ ምን እናርገው? የትኛው ይበጃል? የሚለውን በቅጡ ማጤን ዛሬም ወሳኝ ነው! በወደቀው ላይ ከመፈላሰፍ እንዴት ቀጣዩን በወጉ እንያዘው? ማለት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
ከቶውንም በግሎባላይዜሽን (ትርጉሙ እኳኋን በእርግጥ ባልተረጋገጠው ፅንሰ ሀሳብ ተንተርሶ) አገርን ማሰብ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዳያደርሰን ከልብ ማውጠንጠን ይኖርብናል፡፡ ምዕራባውያን አገሮች እስከዛሬ ያልታየ የፋይናንስ ድንገተኛ አደጋ (Financial Calamity) እየገጠማቸው መሆኑን በዋዛ አንየው! ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እየተንኮታኮተ ያለውን የኢኮኖሚ የበላይነት በተምታታ ብዥታ እንደሚመለከተው መታየት ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ይሄን የውስጥ ድንግርግር በዓለም ዙሪያ በተለይም በአዳጊ አገሮች ላይ በመጫን የንግድ፣ የሽብርተኝነት፣ “የዲሞክራሲን አስፋፋለሁ” መርህ ምህዋር ለማስቀየር መጣጣራቸውን ከመፍራት ይልቅ ማወቅ፣ እጅ ከመስጠት ይልቅ ሉዓላዊነትን ጠንክሮ ማሰብ፤ ደግ መሆኑን የዘመኑ የፖለቲካ ጠበብት እንደሚመክሩ ልብ እንበል፡፡ ዘይት፣ ነዳጅ፣ ማዕድን… ያላቸው አገሮች የሚያስነሱትን ብጥብጥ ያስታውሷል፡፡ የራሳችንን ህዝብ ኢኮኖሚያዊ አሳር ቸል አንበል፡፡ የራሳችንን ህዝብ ፖለቲካዊ ምሬት የራሱ ጉዳይ አንበል፡፡ የራሳችንን ህዝብ አስተዳደራዊ በደል ለሌላ ለማንም ብለን ሳይሆን ለነገ የራሳችን ሰናይ ማንነት ስንል ከጉዳይ እንፃፈው፡፡ የራሳችንን ህዝብ የሞራልና የስነ-ምግባር ምንነት በትምህርት በንቃት፣ በአስተዳደጋዎ አስምህሮት ስራዬ ብለን እንደግፈው፡፡ እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸውን ፍሬ - ጉዳዮች በቅጡ አስበንባቸው ችግሮቻችንን በየደረጃውና በወቅቱ ካልፈታን ለጎረቤት አገሮች እያሳየን ነው የምንለውን የመፍትሄ - አሽነት ሚና የለበለጠ ያስመስልብናል!  ትላንት ሩዋንዳ፣ ሱማሌ፣ ጅቡቲ ወዘተ… በሞፈር - ዘመትነት መሄዳችንን የአንገት - በላይ ያረግብናል፡፡ “የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች” እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡  


Published in ርዕሰ አንቀፅ
  • ባንኩ በሰራተኞቹ አያያዝ ዘረኝነት እንደሚያጠቃው አምኗል
  • ከ3ሺ500 ሰራተኞቹ በከፍተኛ ሃላፊነት የተመደቡት ጥቁሮች 4 ብቻ ነበሩ
  • የባንኩ ቃል አቀባይ ውንጀላው አግባብ አይደለም ብለዋል


       ነዋሪነቱ በአሜሪካ የሆነው ኢትዮጵያዊው የኢኮኖሚ ባለሙያ ዮናስ ብሩ፤ ከአስር አመታት በላይ በከፍተኛ የሃላፊነት የስራ መደብ ተቀጥሮ ይሰራበት የነበረው የአለም ባንክ፣ ያለአግባብ ከስራ በማፈናቀልና የዘረኝነት ጥቃት በማድረስ ለፈጸመበት ወንጀል የ4.1 ሚሊዮን ዶላር (ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ) ካሳ ሊሰጠኝ ይገባል ሲል ክስ መመስረቱን ዋሽንግተን ኢንፎርመር ዘገበ፡፡
“የሚገባኝን የስራ እድገት ተከልክያለሁ ብዬ ለአለቆቼ ተቃውሞዬን በማሰማቴና መብቴን ለማስከበር በመሞከሬ በአለም ባንክ ባለስልጣናት ውሳኔ፡ ያለአግባብ ከስራ ገበታዬ ተፈናቅያለሁ” የሚለው ዮናስ፤ የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ በጥቁሮች ላይ የሚያደርሱትን የዘረኝነት በደልና መድልኦ በመቃወሙ ቅጣት እንደተጣለበትም ተናግሯል፡፡
ባንኩ፣ የሚገባውን የስራ መደብ ያለአግባብ ከመከልከል አልፎ ከስራ በማፈናቀልና ከቀለም ልዩነት ጋር በተያያዘ ላደረሰበት የዘረኝነት ጥቃት ቀደም ሲል ሁለት ክሶችን መስርቶ እንደነበር የገለጸው ዮናስ፤ ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት ግን፣ ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ ባንኩን በነጻ እንዳሰናበተው ጠቅሶ፣ይህም ሌላ ክስ እንዲመሰርት እንዳነሳሳው ይናገራል፡፡
ፍርድ ቤቱ፤ ባንኩን ከተጠያቂነት ነጻ ቢያደርገውም፣ ክሶቹን እንደገና ለመመስረትና ፍትህ ለማግኘት እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጸው ዮናስ፤ ከስራ በመፈናቀሉ ሳቢያ ለደረሰበት የአእምሮ ጭንቀት እና ሳይከፈለው ለቀረው ደመወዝና ጥቅማጥቅም፣ የአለም ባንክ 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን  ዶላር ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል ብሏል፡፡
“ማንም ሰው አለም ባንክን የመሰለ ስመ ገናና ተቋም እንደዚህ አይነት በደል ይፈጽማል ብሎ ለማሰብ ይቸገራል፡፡ ባንኩ የስራ ልምዴን እንዲሰጠኝ ብጠይቅም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ በማናጀርነት ማገልገሌን የሚያረጋግጠውን መረጃ ሊሰጡኝ ባለመፈለጋቸው ሌላ ስራ ለመቀጠር እንኳን አልቻልኩም” ብሏል ዮናስ፡፡
 በ1985 ዓ.ም የአለም ባንክ ባልደረባ ሆኖ መቀጠሩን የሚናገረው ዮናስ፤ ከ6 አመታት በኋላም በባንኩ ስር የሚገኘውን ኢንተርናሽናል ኮምፓሪዝን ፕሮግራም የማሻሻል ሃላፊነት ተሰጥቶት ስራውን በአግባቡ ማከናወኑንና ከ1993 እስከ 2001 ዓ.ም ፕሮግራሙን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን በአግባቡ ሲመራ መቆየቱን ያስታውሳል፡፡ ፕሮግራሙን በየተለያዩ የእስያና የላቲን አሜሪካ አገራት በማስፋፋት ረገድ ተጠቃሽ ስራ ማከናወኑንና ለሰባት አመታት ያህልም ለፕሮግራሙ ገቢ በማሰባሰብ ስራ ላይ መሳተፉን ገልጿል፡፡
 ሆኖም የስራ ልምዱም ሆነ የትምህርት ዝግጅቱ በሚፈቅድለትና ግሎባል ማናጀር ተብሎ በሚታወቀው የባንኩ ከፍተኛ የስራ መደብ ላይ ለመስራት ሲያመለክት፣ የቅርብ አለቃውና የአለም ባንክ ዳይሬክተር የሆነ ሌላ ግለሰብ ያለአግባብ እንደከለከሉት የሚናገረው ዮናስ፤ ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረቡለት አውሮፓውያን በዚህ የስራ መደብ ላይ ጥቁር ሰው ተቀጥሮ ሲሰራ አይተው አያውቁም የሚል እንደነበር ገልጿል፡፡ እንዲህ ያሉት በስራው ላይ እንዳልቀጠር የፈለገው የፕሮግራሙ የውጭ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ለማስመሰል ነው ያለው ዮናስ፤ ቦርዱ ግን ይህ ጉዳይ እንደማይመለከተውና የሃሰት ውንጀላ መሆኑን አረጋግጧል ብሏል፡፡
“ባንኩ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ፣ በዚህ የስራ መደብ ላይ እንዳልመደብ የተደረገው የልምድ ማነስ ስላለብኝ እንደሆነ  ተናግሯል፡፡ ይህ ግን ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን በባንኩ ውስጥ የሚገኘው የስራ አፈጻጸም ልምዴ ያረጋግጣል፡፡ ምክትል ግሎባል ማናጀር ሆኜ በሰራሁባቸው አመታት፣ የተጣለብኝን ከፍተኛ ሃላፊነት በአግባቡ የምወጣ ትጉህ ሰራተኛ እንደነበርኩ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና የቅርብ አለቆቼ መስክረውልኛል፡፡ ይሄን የሚያረጋግጡ ሰነዶች በግል ማህደሬ ውስጥ ቢኖሩም፣ ሰነዶቹ በባንኩ ሃላፊዎች በህገወጥ መንገድ ተሰርዘው በፕሮግራሙ ውስጥ አይነተኛ  ሚና እንዳልነበረኝና የግሎባል ማናጀርነት የሚጠይቀው  ብቃትና ታማኝነት እንደሌለኝ ተደርገው ተጽፈዋል” በማለት ተፈፀመብኝ ያለውን በደል ዘርዝሯል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የአለም ባንክ ቃል አቀባይ፤ ውንጀላው አግባብ አይደለም ከማለት ውጪ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ እንዳልሆኑ የዋሽንግተን ኢንፎርመር ዘገባ ያስረዳል፡፡ “እንዲህ አይነት ክሶች እጅግ አስቸጋሪ ናቸው፤ ነገሩ በሂደት እየተስፋፋና መነጋገሪያ እየሆነ መጥቷል፡፡ ውንጀላው ቀላል አይደለም፡፡ ሰውዬው ስር የሰደደ አመለካከት ነው የያዘው፡፡ በባንኩ አሰራሮች ላይ ያነሳቸውን ጥያቄዎችና ውንጀላዎች በቀላሉ አናያቸውም፤ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፡፡ ከዘረኝነት ጋር ተያይዞ የተነሳውን የሰራተኞቻችን ብዝሃነት  በተመለከተም ጠንካራ አቋም እንደያዝን እንቀጥላለን” ብለዋል የባንኩ ቃል አቀባይ፡፡
“ፍትህ እንዲሰጠኝና ባንኩም እኔን ለስቃይ በመዳረጉ ጥፋተኛነቱን አውቆ እንዲታረም ነው የምፈልገው፡፡ ያለአግባብ ተዛብቶ የተጻፈው የስራ ማስረጃዬ  እንዲስተካከልልኝ ጥያቄ ባቀርብም፣ ባንኩ ግን አሁንም ድረስ ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም። የተዛባውን የስራ ልምድ ማስረጃዬን  ለህዝብ ይፋ ከማውጣት እንዲታቀቡ ብጠይቃቸውም  አሻፈረን ብለዋል፡፡ ይሄም ባለኝ ትምህርትና የስራ ልምድ ሌላ ቦታ ተቀጥሬ እንዳልሰራ እንቅፋት ለመፍጠር ሆን ተብሎ በባንኩ የተሰራብኝ ደባ ነው፡፡” ብሏል ዮናስ ለዋሽንግተን ኢንፎርመር፡፡
የአለም ባንክ በአፍሪካውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን ሰራተኞቹ ላይ በሚያሳየው ያልተገባ የዘረኝነት አመለካከት ከሰላሳ አመታት በላይ ሲተች እንደቆየ የሚናገረው ዮናስ፤ ይሄም ሆኖ ግን ባንኩ በዚህ ድርጊቱ ሳቢያ በህግ ተጠይቆ እንደማያውቅ ገልጿል፡፡ የአለም ባንክ ከተለያዩ 170 የአለም አገራት የተመረጡ 15 ሺህ ያህል ሰራተኞች የሚያስተዳድር ትልቅ ድርጅት እንደሆነ የገለጸው ዋሽንግተን ኢንፎርመር፤ ከተወነጀለበት የዘረኝነት ሃሜት ነጻ እንዳልሆነ የሚጠቁም መረጃ አያይዞ አቅርቧል፡፡ የአሜሪካ የመንግስት ተጠያቂነት ፕሮጀክትን መረጃ ጠቅሶ እንደዘገበውም፣ በ2000 ዓ.ም  በባንኩ ዋና ጽህፈት ቤት ተቀጥረው ይሰሩ ከነበሩት 3ሺ 500 ሰራተኞች መካከል ሙያዊ በሆኑ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ የተመደቡት አራት ጥቁር አሜሪካውያን ብቻ ነበሩ፡፡
ፕሮጀክቱ በሰራው ጥናት፣ ጥቁሮች በባንኩ የአመራርነት ቦታዎች ላይ የመመደብ እድላቸው አነስተኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በዚህ ፕሮጀክትና በራሱ በአለም ባንክ የተሰሩ ጥናቶችም፣ በባንኩ ውስጥ ከቀለም ልዩነት ጋር በተያያዘ በጥቁሮች ላይ የዘረኝነት ጥቃትና መድልኦ ስር መስደዱ ተረጋግጧል፡፡ ጥቁር የባንኩ ሰራተኞች ወደከፍተኛ የአመራርነት ቦታ እንዳይመጡና እድገት እንዳያገኙ ጫና እንደሚደረግባቸውም ተጠቁሟል፡፡
የባንኩ የቀድሞ የስራ ባልደረባ ፊሊስ ሙሃመድ በአንድ ወቅት ለንባብ ያበቃችውን መረጃ በመጥቀስ ዋሽንግተን ኢንፎርመር እንደዘገበው፤ በ1952 ዓ.ም በባንኩ የአንድ ክፍል ሃላፊ የነበሩ ግለሰብ፣ ሰራተኞችን ባሳተፈ ስብሰባ ላይ የባንኩን ዘረኝነት የሚያረጋግጥ ንግግር አሰምተዋል፡፡ “ጥቁሮች ደደብ የሂሳብ ባለሙያዎችን ነው የሚያፈሩት፤ የእኛ ክፍልም የቦዘኔዎች መፈንጫ ጉራንጉር መምሰል ስለማይፈልግ ብዙ ጥቁሮችን ቀጥሮ አያሰራም። ጥቁሮች እዚያው በአፍሪካ ጉራንጉር ነው መኖር ያለባቸው” በማለት፡፡
 ዋሽንግተን ኢንፎርመር ያቀረበው ሌላው መረጃም፣ በ1990 ዓ.ም የተካሄደ አንድ የአለም ባንክ ውስጣዊ ስብሰባ ሚስጥራዊ ቃለጉባኤ፣ ጥቂት የባንኩ ማናጀሮች “ጥቁሮች የበታች ናቸው” ብለው እንደሚያስቡና ጥቁሮች ከአፍሪካ ውጭ የመስራት ችሎታቸው አናሳ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ፣ በአብዛኛው በዚያው በአህጉራቸው አካባቢ እንዲሰሩ እንደሚደረግ  አመልክቷል፡፡
ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት የሆነው ዮናስ ብሩ፤ የንጉሳዊው አገዛዝ አክትሞ ደርግ ወደ ስልጣን በመጣበት ጊዜ ወደ አሜሪካ መሄዱንና በተለያዩ የጉልበት ስራዎች ላይ ተሰማርቶ ለአመታት ደፋ ቀና ብሎ በመስራት ራሱን አስተምሮ፣ ከጆርጅ ማሰን ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪውን መቀበሉን ለዋሽንግተን ኢንፎርመር ተናግሯል፡፡

Published in ዜና
  • መንግስት የነዳጅ ዋጋን ማረጋጋት አለበት” (ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ብሩህ ተስፋ)
  • ባለፉት 8 ዓመታት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከአራት እጥፍ በላይ አድጓል
  • የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መንግስት ለዜጎቹ ግድ ማጣቱን አመላካች ነው፡፡(የከተማዋ ነዋሪ)

የስምንት ዓመት የዋጋ ንረት
    1998         2006
ቤንዚን             6.57        20.47
ነጭ ጋዝ            3.45        15.75
ታክሲ (አጭር ርቀት)        0.60ሳ        1.50
ታክሲ (ረዥም ርቀት)    1.25        3.00
አንበሳ አውቶብስ        0.50ሳ        300% ጭማሪ

አቶ መስፍን ወርቅነህ በመንግስት መ/ቤት የንብረት አስተዳደር ክፍል ውስጥ ተቀጥረው መስራት ከጀመሩ ወደ 18 ዓመት ገደማ አስቆጥረዋል፡፡ ሥራ ሲጀምሩ የወር ደመወዛቸው 720 ብር ነበር፡፡ በሥራ ዘመናቸው ለሦስት ጊዜ ያህል የደረጃ ዕድገቶችና የደመወዝ ጭማሪ ዕድሎችን አግኝተዋል፡፡ በ18 ዓመት ጊዜ ውስጥ ደሞዛቸው 1690 ብር ደርሷል፡፡
ከ15 ዓመት በፊት ትዳር የመሰረቱት በ280 ብር ከግለሰብ በተከራዩት ቤት ውስጥ ሲሆን ሦስት ልጆቻቸው የተወለዱትም እዚሁ ቤት ውስጥ ነው፡፡ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ አከራያቸው ድንገተኛ የሃምሳ ብር ጭማሪ ሲያደርጉባቸው ክው ብለው ደነገጡ፡፡ የከተማው ዳርቻ አካባቢ አነስተኛ የኪራይ ቤት ማሰስ ጀመሩ።  በመጨረሻም አየር ጤና የተባለው ሰፈር በ200 ብር የኪራይ ቤት አገኙና ቤተሰባቸውን ይዘው ገቡ፡፡ አቶ መስፍን ከከተማ ወጣ ብለው ቤት የተከራዩት፣ወጪያቸውን በመቀነስ የሚያገኟትን ደሞዝ አብቃቅተው ሦስቱን የአብራካቸውን ክፋዮች ሳይርባቸው ሳይጠማቸው አሳድጋለሁ በሚል ነበር፡፡ ጊዜው ግን ከእሳቸው ጋር እልህ የተጋባ መሰለ፡፡ ከዓመት ዓመት ኑሮው ወደ ላይ ይተኮስ ጀመረ ይላሉ፤ አዛውንቱ፡፡     
ከአየር ጤና ካዛንቺስ ሱፐር ማርኬት አካባቢ እሚገኘው መ/ቤታቸው ለመድረስ ሁለት አንበሳ አውቶቡሶችን መጠቀም ነበረባቸው፡፡ የአንድ ቀን የደርሶ መልስ ወጪያቸው 3 ብር ሲሆን በወር 80 ብር ገደማ ለትራንስፖርት ያወጣሉ፡፡ አንዳንዴ ከረፈደባቸው ወይ ከቸኮሉ  ከ5-6 ብር ለማውጣት ይገደዳሉ - በታክሲ ለመሄድ፡፡ የቤታቸውና የመሥሪያ ቤታቸው ርቀት ለምሣ ወደቤት መሄድን ፈፅሞ የሚያሳስብ አይደለም፡፡ መ/ቤታቸው አቅራቢያ ባለች አነስተኛ ምግብ ቤት ከ8-10 ብር እያወጡ  ምሳቸውን የሚመገቡት አቶ መስፍን፤ የምሳ ወርሃዊ ወጪያቸው ከ180-200 ብር ይደርስ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
በልጆች ት/ቤት በኩል የተገላገሉ ይመስላሉ። ሁሉም  በመንግስት ት/ቤት ነው የሚማሩት፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በአመቱ መጀመሪያ ላይ ለትምህርት መሳሪያዎችና ለዩኒፎርም ማሰፊያ የሚጠየቁት ገንዘብ ወገብ ይቆርጣል። የቱንም ያህል ፈተናና ውጣ ውረድ ቢበዛባቸውም ሁሉን ተቋቁመው ወደፊት እንዲጓዙ የሚያደርጋቸው ተስፋቸው ነበር፡፡ መቼም ቢሆን የተሻለ ነገን ከማለም ቦዝነው አያውቁም፡፡ አስደንጋጩ የኑሮ ውድነት ግን ህይወታቸውን አጨለመባቸው፡፡ ህልምና ተስፋቸውን ነጠቃቸው፡፡
ለኑሮ ውድነቱ መባባስ፣ ለሸቀጦች ዋጋ መናር፣ ለትራንስፖርት ዋጋ በሁለትና ሦስት እጥፍ መጨመር፣ ለነዋሪው ኪስ መራቆት፣ ለችግርና ጉስቁል መጋለጥ፣ ወዘተ… ሰበቡ ልጓም ያጣው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ነው። ሌላው ቀርቶ መንግስት እንኳ በሰፊ እጁ ስላለቻለው “ድጎማውን ትቼ አለሁ” ብሎ በይፋ እጅ ሰጥቷል። ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በነዳጅ ዋጋ ላይ የተደረገው ተከታታይ የዋጋ ጭማሪ የአቶ መስፍንን ህይወት ብቻ አይደለም ያናጋው፡፡ እንደሳቸው ያሉ ሚሊዮኖችን ኑሮ አቃውሷል፡፡ የሚሊዮኖችን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮም አዛብቷል፡፡ አቶ መስፍን፤ ከ10 ብር በማይበልጥ ዋጋ ምሳቸውን ይበሉበት የነበረው ምግብ ቤት፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዓይናቸው እያየ 40 እና 50 ብር ገባ፡፡ የዛሬው ብቻ ሳይሆን የነገው ጭምር ያሳስባቸው ጀመር፡፡ “አንዳንዴ የምንኖረው በተአምር ነው የሚመስለኝ፤ ምኑ ተምኑ ተደርጐ ከወር ሊደርስ እንደሚችል ማሰቡም ከባድ ነው፡፡ ተዉኝ እባካችሁ… ለዜጎች ግድ ያጣ መንግስት ነው ያለን፡፡ ብናልቅስ ምን ገዶት ብላችሁ!” ይላሉ  አቶ መስፍን - የኑሮ ውድነቱ የወለደውን ብሶታቸውን ሲተነፍሱ፡፡
የአለማቀፉን የነዳጅ ዋጋ ውጣ ውረድ ተንተርሶ፣ የንግድ ሚኒስቴር በወሩ መጨረሻ የሚያወጣው የነዳጅ ዋጋ ክለሣ፣ በ8 አመት ውስጥ ከሶስት እጥፍ በላይ መጨመሩን ያመለክታል፡፡ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከግንቦት 1998 ዓ.ም ጀምሮ በፍጥነት እየጨመረ የመጣው የአለማቀፉ የነዳጅ ዋጋ፣ በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦትና የዋጋ ተመን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳርፏል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ የበርሜል ነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ በዚያው ዓመት በተደረገው የዋጋ ክለሣ፣ የአዲስ አበባ የተራ ቤንዚን መሸጫ ዋጋ፣ በሊትር 6 ብር ከ57 ሣንቲም ገደማ የነበረ ሲሆን ታሪፉ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደገና ተሻሽሎ  በታህሳስ 1999 ዓ.ም 7 ብር ከ75 ሳንቲም  ሆነ፡፡ በ8 ወር ጊዜ ውስጥ በሊትር እስከ 1ብር ከ20 ሣንቲም የሚደርስ ጭማሪ ተደርጓል ማለት ነው፡፡ በወቅቱ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በህብረተሰቡ የእለት ተእለት ኑሮ ላይ የጐላ ጫና አሳርፏል ለማለት ባያስደፍርም፣ ጭማሪው ቀደም ካሉት አመታት አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ነበር፡፡
ከአመት በኋላ በንግድ ሚኒስቴር በተደረገው ክለሳ፣ የነዳጅ ዋጋ ወደ 9 ብር ከ60ሣ. አድጓል፡፡ ከቀድሞው ዓመት 1 ብር ከ85 ሣንቲም ጭማሪ በማሳየት ማለት ነው። የ2001 ዓ.ም የነዳጅ ዋጋ ደግሞ ቀደም ካለው ዓመት 1 ብር ከ40 የሚደርስ ቅናሽ እንዳሳየ የሚኒስቴር መ/ቤቱ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ሰኔ 2001 የተከለሰው የነዳጅ ዋጋ እንደሚያመለክተው፤ ቤንዚን በሊትር 8 ብር ከ95 ሣንቲም ገደማ ሲሆን ከሁለት ወር በኋላ በጳጉሜ 2001 በተደረገው ክለሳ፣ አዲስ አበባ ላይ በሊትር የ2 ብር ገደማ ጭማሪ በማሳየት ወደ 10 ብር ከ93 ሣንቲም ተመነደገ፡፡ ከአንድ አመት በኋላ በህዳር 2003 ዓ.ም በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበው የቤንዚን ዋጋ፣ 14 ብር ከ87 ሣንቲም የደረሰ ሲሆን ከአምስት ወር በኋላ በአብዛኛው የክልል ከተሞች በሊትር ከ22 ብር በላይ ሲሸጥ፣ በአዲስ አበባ የ6 ብር ጭማሪ ተደርጐበት   በሊትር 20 ብር ከ94 ሣንቲም ገባ። ይህም በ8 አመት ውስጥ በጥቂት ወራት ልዩነት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ወቅት መሆኑን ያመለክታል፡፡
2004 እና 2005 ዓ.ም ከሌሎቹ አመታት በንፅፅር የነዳጅ ዋጋ የተረጋጋበት ወቅት ነበር፡፡ መጠነኛ ቅናሽም አሳይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ከ18 ብር ከ75 ሣንቲም እስከ 19 ብር ከ45 ሣንቲም ባለው ዋጋ መካከል ሲዋልል ቆይቷል፡፡ ዘንድሮ በ2006 ዓ.ም የየካቲት ወር የቤንዚን ዋጋ በሊትር 20 ብር ከ47 ሣንቲም ተተምኗል፡፡
በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል፣ እንደ እለት ተእለት ፍጆታው የሚጠቀምበት ነጭ ጋዝ (ላምባ)፤ በ1998 አዲስ አበባ ላይ በሊትር 3 ብር ከ45 ሲሸጥ፣ በየካቲት 2006 ዓ.ም 15 ብር ከ75 ሣንቲም እየተሸጠ ነው፤ በአምስት እጅ ጨምሮ፡፡
የንግድ ሚኒስቴር ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በየወሩ መጨረሻ ላይ የሚያደርገውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣንም የትራንስፖርት ዋጋ ማሻሻያ እያደረገ ነው፡፡ የታሪፍ ጭማሪው በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሃይገር ባሶች፣ የከተማ አውቶቡሶችና ታክሲዎችን የሚመለከት ሲሆን አንበሳ አውቶቡሶች ከ0.50 ሳንቲም ታሪፍ ተነስተው እንደየርቀታቸው ከ300% በላይ ጭማሪ አድርገዋል፡፡ በ1998 ዓ.ም የአጭር ርቀት የታክሲ ተመን 65 ሳንቲም፣ የረዥም ርቀት 1.25 ሳንቲም የነበረ ሲሆን አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ክፍያው ወደ 95ሣ. እና 1.65 ሳንቲም ከፍ ብሏል፡፡ በየጊዜው በሚደረገው የዋጋ ማሻሻያ መሠረትም ታሪፉ እየጨመረ ሄዶ፣ በያዝነው የካቲት ወር የአጭር ርቀቱ 1.50 ሳንቲም፣ ረዥም ርቀቱ 3.00 ብር ሆኗል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በአገሪቱ ኢኮኖሚና በህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ በተመለከተ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም መምህር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ብሩህ ተስፋ፤ በየጊዜው በሚጨምረው የነዳጅ ዋጋ በይበልጥ የሚጐዳው በቋሚ ደመወዝ የሚተዳደረው የህብረተሰብ ክፍል ነው ይላሉ፡፡
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከአለም የነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ እንደሚከሰት የጠቆሙት ዶክተሩ፤ መንግስት ሌላውን ዘርፍ እየጎዳ በነዳጅ ላይ ድጎማ ያደርግ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር በሁሉም ሴክተር ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ እንደማይቀር ጠቁመው፤ በዚህ ተጎጂ የሚሆነው በተለይ በቋሚ ደመወዝ የሚተዳደረው የህብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “በዓለም የነዳጅ ዋጋ ስለጨመረ እኛም መጨር አለብን በማለት መንግስት በየጊዜው በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገው ጭማሪ አያዋጣም” የሚሉት ባለሙያው፤ የነዳጅ ዋጋው በጨመረ ቁጥር የዋጋ ግሽበቱ እየጨመረ መሄዱ በህብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተሰብስበው እንዲመክሩበትና መፍትሄ እንዲፈልጉለት ማድረግ ተገቢ ነው” ሲሉም ይመሰክራሉ፡፡ በዋናነት የነዳጅ ዋጋን የማረጋጋት ኃላፊነት የመንግስት መሆኑንም ያሰምሩበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው ህብረተሰብ አቀፍ ዘርፍ በመሆኑ መንግስት ሊቆጣጠረው የሚችለው ነው ያሉት ዶክተሩ፤ የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር ነጋዴው በሚሸጠው ዕቃ ላይ ዋጋ ጨምሮ በመሸጥ ጭማሪውን ሊቋቋመው እንደሚችል ጠቅሰው፣ ሸማቹ በተለይም ቋሚ ገቢ ያላቸው የመንግስት ሰራተኞችና ጡረተኞች ግን ለጉዳት እንደሚጋለጡ ተናግረዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኞች ሲባልም የጦር ኃይሎችና የፖሊስ አባላትን እንደሚያካትት፣ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎችም በዋጋ ንረቱ እንደ ሚጎዱ በመግለፅ ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊታይ ይገባዋል ብለዋል፡፡
አገሪቱ በዓመት ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ነዳጅ እንደምታስገባ የጠቆሙት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚደረገውን ጭማሪ ለመግታት ሌላው አማራጭ የነዳጅ ፍጆታን መቀነስ እንደሆነ ጠቁመዋል። በከፍተኛ መጠን ነዳጅ የሚጠቀሙት የመንግስት መስሪያቤቶች ሲሆኑ መኪኖች፣ ጄኔሬተሮች፣ ግድቦችና መሰል ነገሮች የሚሰሩት በነዳጅ በተለይም በናፍጣ በመሆኑ ይህንን ፍጆታ መቀነስ የሚቻልበት መንገድ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ሌላው ምሁሩ አማራጭ ነው ያሉት ጉዳይ የነዳጅ ፍለጋውን አጠናክሮ መቀጠል ሲሆን ነዳጅን እየደጎሙ መቀጠሉ አዋጪ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ማሻቀቡ ሌላው ምክንያት ነው ያሉት የፍጆታ መጠን መጨመሩ ሲሆን አሁን አገሪቱ ውስጥ ባለው ሁኔታ እየተሰሩ ያሉት መሰረተ ልማቶች፤ ማሽኖችና መሳሪያዎች የሚወስዱት የነዳጅ ፍጆታ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ አገራችን በአብዛኛው ነዳጅ የምታስገባው ከኩዌት መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለመግታት መንግስት ሊያስብበት ይገባል ይላሉ። የልማት ስራዎች ሲሰሩም የህዝቡን ጥቅምና ፍላጎት ሳይነኩ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው፤ “ከአቅም በላይ የሚሰራ ልማት ጫናው በህብረተሰቡ ጫንቃ ላይ ያርፍና ህብረተሰቡ ይበልጥ እየተቀየመ ከመጣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ይፈጥራል” ብለዋል፡፡ በእሳቸው ዘመን ከንጉሱ ጊዜ ተቃውሞ ለለውጡ ዋንኛ መንስኤ የነበረው የታክሲ ነጂዎች በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት ያስነሱት ተቃውሞና ያደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ መሆኑንም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ አስታውሰዋል፡፡

Published in ዜና
Page 6 of 13