በቀጣዩ ዓመት ከአገሪቱ የመድኀኒት ፍጆታ ግማሽ  ያህሉን በአገር ውስጥ ለማምረት ታቅዷል
አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በግል የጤና ተቋማት ውስጥ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት መጀመሩ ተገለፀ፡፡ ድሃውን ተጠቃሚ የሚያደርግ የግል የጤና ተቋም ቀጣይነቱ አጠያያቂ ነው ተብሏል፡፡
“The private Health Sector in Ethiopia at a Crossroads” በሚል ሰሞኑን ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ እንደተገለፀው፤ የግሉ የጤና ሴክተር ከመንግስት የጤና ዘርፍ ጋር በትብብር በመስራት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል፡፡ አብዛኛ ህብረተሰብ በግል የጤና ተቋማት ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት አቅም የሌለው በመሆኑ፣ የግሉን የጤና ዘርፍ በተለያዩ መንገዶች በማገዝ አገልግሎቱን ለድሃው ህብረተሰብ ለመስጠት የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዲስ ታምሪ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤የመንግስትና የግሉ የጤና ተቋማት በትብብር በመሥራት በአገሪቱ የጤናው ዘርፍ የሚታየውን እጥረት ለመቅረፍ ጥረት ያደርጋሉ። የግሉ የጤና ዘርፍ ከመንግስት በሚደረግለት ድጋፍና ትብብር አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ፣ድሃውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መንግስት በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ የሚጀምረው የግሉንም ሆነ የመንግስትን የጤና ተቋማት ደረጃ የሚያወጣው መመሪያ ተግባራዊ መሆን ይህንን አሰራር ለመቆጣጠርም እንደሚረዳ ዶ/ር አዲስ ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ በጤናው ዘርፍ እየተገበረች ላለው ሥራ የግሉ የጤና ዘርፍ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት እደለም ያሉት ዶክተሩ፤ ይህንን አስተዋፅኦ የበለጠ ለማሳደግ እንዲችል ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል፡፡ የግሉና የመንግስቱ የጤና ተቋማት በትብብር ድሃውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማገልገል የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም ሲሉ ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡
በቀጣዩ አመት አገሪቱ ከሚያስፈልጋት የመድኀኒት ፍጆታ ግማሽ ያህሉ በአገር ውስጥ በሚገኙ የመድኀኒት ማምረቻ ፋብሪካዎች የሚመረቱ እንደሆኑ ዕቅድ መያዙንም ዶክተሩ በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና

635 የመከላከያ ምስክሮች በተከሣሾች ተቆጥረዋል
በትናንትናው እለት ሙስሊሙ ህብረተሰብ ተቃውሞ አሰምቷል

በአወሊያ ት/ቤት መነሻነት “ድምፃችን ይሠማ” በሚል ከተፈጠረው መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ በእነ አቡ በከር መሃመድ መዝገብ ስር፣ በሽብር ወንጀል የተከሰሱት 18 ግለሰቦች ያቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ ጭብጥ ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤቱን አከራክሯል፡፡
የተለያዩ የሽብር ተግባሮች ውስጥ ተሳትፈዋል ተብለው ክስ የቀረበባቸው 18 ተከሳሾች፣ ቀደም ሲል በአቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ማስረጃ ይከላከሉ ሲል ፍ/ቤት ብይን መስጠቱን ተከትሎ ይከላከሉልናል ያላቸውን 635 የሰው ምስክሮች ቆጥረዋል፡፡
በትናንት በስቲያው ችሎት ተከሳሾች በጠበቆች አማካይነት ከቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ ጭብጥ ውስጥ አቃቤ ህግ የሚቃወማቸውን ነጥቦች በዝርዝር ጠቅሶ አቅርቧል፡፡ ከተጠቀሱት የመከላከያ ማስረጃ ጭብጦች መካከልም “ሃይማኖታዊ ቃላትን የሃይማኖት አባቶችን አቅርበን እናስተነትናለን” ማለታቸው  ፍ/ቤቱን በስፋት አከራክሯል፡፡
ቀደም ሲል በአቃቤ ህግ የማስረጃ አቀራረብ ወቅት ሲጠቀሱ ነበር ከተባሉት ሰደቃ፣ ጅሃድ፣ አዛን፣ አህባሽ እና ሌሎችም ሃይማኖታዊ ትርጉም አላቸው ለተባሉ ቃላት ሙያዊ ትንታኔ እናሰጥበታለን መባሉን የተቃወመው አቃቤ ህግ፤ “የእነዚህ ቃላት ትርጓሜና ትንታኔ የሚቀርብበት ምክንያት የለም፣ በዚህ ችሎት እየታየ ካለው ጉዳይ ጋርም አይገናኝም“ ሲል አመልክቷል፡፡ ፍ/ቤቱም በማጣሪያ ጥያቄው እነዚህን ቃላት ለማስተንተን ሙያዊ ማስረጃ ማቅረብ ለምን ያስፈልጋል ሲል የጠየቀ ሲሆን የተከሳሽ ጠበቆች በሰጡት ምላሽ፤ ቀደም ሲል አቃቤ ህግ ማስረጃውን ሲያቀርብ “አህባሽ የሚባል ሃይማኖት የለም” በማለቱ ሃይማኖቱ መኖሩን ለማስረዳት፣ ወሃቢያን በቀጥታ ከሽብርተኝነት ጋር አያይዞ በማስረዳቱ ስለወሃብያ ምንነት ለማስረዳት፣ አዛን በማይደረግበት ጊዜ አዛን አድርገው ህዝቡን ቀስቅሰዋል በማለቱ አዛን መቼ እና እንዴት ይደረጋል የሚለውንና ሌሎች ሃይማኖታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልጋቸውን ተንትኖ ለማስረዳት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ እነዚህን ቃላት ሽፋን አድርገው ወንጀል ፈፅመዋል ስለተባለም ትክክለኛ ፍቺውን ለማስገንዘብ ነው ብለዋል፡፡
በተከሣሾች ማስረጃ ውስጥ ግልፅነት ይጎድላቸዋል ተብለው በአቃቤ ህግ ከተጠቀሱት መካከልም አቃቤ ህግ “የኡስታዞች (አስተማሪዎች) ቡድን ብሎ የጠራው የአድማ ቡድን አይደለም፤ ሃይማኖታዊ እውቀትን ለማስፋፋት የተደራጀ ነው” ያሉ ሲሆን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ “አድማ ለማድረግና ወንጀል ሊሰሩ የተደራጁ ናቸው አላልኩም” ሲል አቃቤ ህግ ተከላክሏል፡፡ በዚህ ጭብጥ ላይ ክርክር እንዳይደረግበትም አመልክቷል- አቃቤ ህግ፡፡
ሌላው “እኛ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ለመሆን ተመርጠን ችግሩን ለመፍታት በመንግስትና በህዝቡ መካከል እንደ ድልድይ ስናገለግል ነበር፡፡” በማለት አግኝተናቸዋል ያሏቸውን ባለስልጣናት ስም ዝርዝር በመከላከያ ማስረጃቸው መዘርዘራቸውን በመጥቀስ፤ አቃቤ ህግ ግልፅ አይደለም ሲል ተከራክሯል፡፡ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ከህዝበ ሙስሊሙ ተመርጠው የሙስሊሙን ጥያቄ ለመንግስት ለማቅረብ የተወከሉ መሆኑን ለማስረዳት ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የ1997 ዓ.ም የምርጫ ቀውስን ተከትሎ የቅንጅት መሪዎች ጉዳይ በታየበት በአቃቂ 08 ቀበሌ አዳራሽ በዋለው በዚህ ችሎት፤ ከአቃቤ ህግ እና ከጠበቆች ክርክር ባሻገር ፍ/ቤቱ በማስረጃ ጭብጥ ዝርዝሩ ላይ ቀኖች በሚገባ አልተገለፁም የሚሉና የተለያዩ የማጣሪያ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆችም የተለያዩ የቀን ማስተካከያዎችን አድርገዋል፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩ የተከሳሾች ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች የታደሙበት ችሎቱ፤ በዚህ የማስረጃ ጭብጥ ክርክር ላይ የጠዋቱ ጊዜ ባለመብቃቱ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለከሰዓት በኋላ የቀጠረ ሲሆን ችሎቱ ከሰዓት በኋላ ቀጥሎ ዳኞች ጉዳዩን መርምረው ውሳኔ ለመስጠት ሰዓት እንዳልበቃቸው በመግለፅ፤ መዝገቡን ለፊታችን ማክሰኞ ቀጥረዋል፡፡ በእለቱ ዳኞች ተቀይረው ስለነበር  ቅያሬውን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የቀኝ ዳኛው፤“መደበኛ ዳኞች እክል ስለገጠማቸው ሂደቱ እንዳይቋረጥ ነው እኛ የተገኘነው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በትናንትናው እለት መርካቶ በሚገኘው ታላቁ አንዋር መስጊድ በተከናወነው የጁማ ሶላት ስግደት ሥነሥርዓት ላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
ለደቂቃዎች በቆየው በዚህ የተቃውሞ ድምጽ ነጭ ሪቫን በሁለት እጃቸው ወደ ላይ ዘርግተው በማውለብለብ አሜን! አሜን! አሜን! የሚለውን ቃል ሲያስተጋቡ እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል፡፡ በቦታው ፖሊስ የነበረ ቢሆንም ተቃውሟቸውን ባሰሙ የእምነቱ ተከታዮችና በፖሊስ መካከል ምንም ግጭት አልተፈጠረም፡፡   

Published in ዜና

ቅሬታቸውን ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ገልጸዋል

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በኾኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነትና ሥርዐት እንዲማሩ፣ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን በማቀናጀት ሞያዊ ድጋፍ እንዲያበረክቱ በማስተባበር ላይ የሚገኘውን ማኅበረ ቅዱሳንን በአሸባሪነት በመፈረጅ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት ጠቅላላ ሀብቱና ንብረቱ የሚታገድበት ውሳኔ እንዲተላለፍ በመንግሥትም በኩል እርምትና ርምጃ እንዲወሰድበት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአድባራት አስተዳዳሪዎች መግለጫ አውጥተውበታል በተባለው ስብሰባ ጉዳይ ኹለት የቅ/ሲኖዶስ አባላት ለከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊዎች ቅሬታቸውን ማሰማታቸው ተገለጸ፡፡
የቅ/ሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስንና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን በስም የጠቀሱት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች፣ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች እንደኾነ ቢገልጹም የሓላፊዎቹን ስም ከማሳወቅ ተቆጥበዋል።
ቤተ ክርስቲያኒቱ በፀረ ሙስናና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከመንግሥት ጋራ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መወሰኗን ሊቃነ ጳጳሳቱ አስታውሰው፣ በዚህም መሠረት ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን ለማረምና ለማስተካከል ጥረት እያደረገች ቢኾንም ባለሥልጣናቱ ከማን ጋር መሥራት እንዳለባቸው በትክክል አለመለየታቸውንና ግንኙነቱም ሙሰኞችን በአይዟችኹ ባይነት የሚያበረታታ እንደኾነ መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡
ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅሬታቸውን በዚህ መልኩ ለባለሥልጣናቱ ለማቅረብ ያስገደዳቸው የአድባራት አስተዳዳሪዎቹ፣ ‹‹ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ለአድማ ያነሣሣል፤ በሀገርና በቤተ ክርስቲያን ላይ ሁከትና ሽብር እንዲፈጠርና ሰላም እንዲደፈርስ ያደርጋል›› ባሉት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚወሰደው አስተዳደራዊ ርምጃ በፀረ ሽብር ሕጉ መሠረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁበት መግለጫቸው ነው፡፡
የመንግሥት የተለመደ እገዛ እንዳላቸው በአጽንዖት የጠቀሱት አስተዳዳሪዎቹ በዚሁ መግለጫቸው፣ መንግሥት በፀረ ሽብር ሕጉ ታሳቢነት ገለልተኛ ኦዲተር መድቦ በማኅበሩ ላይ የሀብትና ንብረት ቁጥጥር የማካሔድ ድጋፉ እንዳይለያቸው ያስተላለፉት ጥሪ በሌላቸው ሕጋዊነትና ውክልና የቀረበ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በራስዋ መንገድ ማከናወን በሚገባት ተግባር ላይ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝና ለውጭ ተጽዕኖ አሳልፎ የሚሰጥ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡
በመንበረ ፓትርያርኩ ከተገኙት የመንግሥት ሓላፊዎች ጋራ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እንደተካሔደ በተገለጸው የኹለትዮሽ ውይይት፣ ማኅበረ ቅዱሳንን በመቃወም ሰበብ የወጣው የአስተዳዳሪዎቹ መግለጫ ዋነኛ ዓላማ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ወስና የምታካሒደውን የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ሒደት መጋፋት ነው ተብሏል፡፡  መላውን የሀገረ ስብከቱን አድባራት አገልጋዮች  ለመወከል የማይበቁ ጥቂት ግለሰቦችን በመያዝ ይደረጋል የተባለው ይኸው እንቅስቃሴም ‹‹የት እንደሚያደርስ እናየዋለን›› የሚሉ ንግግሮች ጭምር ከሊቃነ ጳጳሳቱ የተሰሙበት እንደነበር ምንጮቹ አስታውቀዋል፤ ጉዳዩም በመጪው ግንቦት በሚካሔደው የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዓቢይ መነጋገርያ መኾኑ እንደማይቀር ተጠቁሟል፡፡
ከሀገረ ስብከቱ አድባራት የተውጣጡ ናቸው የተባሉ አስተዳዳሪዎች ያደረጉት ስብሰባ፣ አስተባባሪዎቹ ከፓትርያርኩ ተሰጥቶናል ከሚሉት ፈቃድ በቀር በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ዘንድ በይፋ የታወቀና የተፈቀደ እንዳልነበረ ምንጮቹ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳንን በሁከትና ሽብር ለሚከሱ በቂ ሕጋዊነትና ውክልና የላቸውም ለተባሉ አካላት ፓትርያርኩ የሰጡትን የስብሰባ ፈቃድ፣ በቅርቡ ማኀበሩ አገር አቀፍ የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ  እንዳያካሒድ ከተጣለበት እገዳ ጋር ያነፃፀሩ ታዛቢዎች፣ ሁኔታው የፓትርያርኩን ርምጃዎች መርሕ አልባነት የሚያጋልጥ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር መተዳደርያ ደንብ ያለውና ግልጽ ተልእኮ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ማኅበር፣ህልውናና አገልግሎት በግልጽ አስተዳደራዊ ጫና ውስጥ መግባቱን  እንደሚያመለክት ታዛቢዎቹ ያምናሉ፡፡
ከመዋቅር፣ ከሀብትና ንብረት ቁጥጥር ጋራ በተያያዘ በማኅበሩ ላይ የሚቀርቡት ውንጀላዎች፣ በፀረ አክራሪነት ስም የሚናፈስበትን ፕሮፓጋንዳ በማጠናከር ፖሊቲካዊ ርምጃ እንዲወሰድበት ፍላጎት ያላቸውን አካላት ምኞት በጉልሕ እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ማኅበሩ ሃይማኖቱን የሚጠብቅ፣ ቤተ ክርስቲያኑን የሚከባከብና ሀገሩን የሚወድ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ያለውን ዓላማ የሚረዱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምእመናንና የመንግሥት አካላትም የተቃዋሚዎቹን አቋምና መግለጫ በጥንቃቄ እንዲመለከቱትም አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናና ትውፊት ውጭ ነው በተባለ የሌላ እምነት አስተምህሮ የተነሳ  በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት መካከልና በደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት አባላት ውስጥ ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ እንደገባ እየተገለጸ ነው፡፡
ከኮሌጁ ውጭ ከሚገኙና በቅ/ሲኖዶስ ከተወገዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋር የዓላማና የጥቅም ግንኙነት መሥርተዋል በተባሉ ጥቂት ደቀ መዛሙርት አማካይነት በኮሌጁ ውስጥ ከመንጸባረቅ አልፎ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ነው የተባለው ይኸው አስተምህሮ፣ አስተዳደራዊ መፍትሔ እንዲበጅለት የደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት ጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ለኮሌጁ አስተዳደር ያቀረበው ጥያቄ እስከ አሁን ምላሽ አለማግኘቱ  ውጥረቱን የበለጠ እንዳባባሰው ለአዲስ አድማስ የደረሰው መረጃ አመልክቷል፡፡
የአስተምህሮው ውዝግብ አፋጣኝ መፍትሔ አለማግኘቱ ከደቀ መዛሙርቱ አልፎ የምክር ቤት አባላትን ለሁለት እንደከፈለ ተገልጧል፡፡ ኮሌጁንና ደቀ መዛሙርቱን በቅንነትና በትጋት ለማገልገል በደቀ መዛሙርቱ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠውና ከፍተኛ ሓላፊነት የተጣለበት የደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት፣ ‹‹ከልማቱ ጥፋቱ አመዝኗል›› ያሉት ጸሐፊውና አንድ የአመራር አባሉም ራሳቸውን ማግለላቸው ታውቋል፡፡
‹‹ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ትውፊት ውጭ የኾነ የኑፋቄ ትምህርት ሲዘራ ድምፀ ተዓቅቦ ከማድረግ ባሻገር ችግር አለባቸው ከሚባሉት ደቀ መዛሙርት ጎን ተሰልፈው ኮሌጁንም ኾነ ሓላፊነት የሰጠንን ደቀ መዝሙር በቅንነት እንዳናገለግል የአንዳንድ መማክርት አባላት ተግባር አውኮናል›› ያሉት ሁለቱ አባላት፤ በዚህ ሳምንት ለኮሌጁ ዋና ዲን ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ምክር ቤቱ የችግሩ ተባባሪ በመኾኑ ከሓላፊነቱ ታግዶ ጉዳዩ እንዲጣራና እምነታቸውና ሥነ ምግባራቸው በተመሰከረላቸው ደቀ መዛሙርት እንዲተካ ጠይቀዋል፡፡
‹‹የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ እየበሉ፣ በጀቷን አውጥታ እያስተማረቻቸው የሌላ እምነት የሚያራምዱ›› ያሏቸውን ወገኖች አጥብቀው እንደሚቃወሙ የገለጹ የደቀ መዛሙርት ተወካዮች በበኩላቸው፣ ኮሌጁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት ለመጠበቅና ለማስፋፋት የቆመ  በመኾኑ አስተዳደሩ፣ በቃል፣ በድምፅና በጽሑፍ የሚቀርቡለትን ማስረጃዎች መርምሮ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡

Published in ዜና

በነገው እለት በትግራይ ክልል በእንደርታ ኪዊሃ፣ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያካሂድ የገለፀው ዓረና ፓርቲ፤የትግራይ አርሶ አደሮች በካድሬዎች መብታቸው እየተረገጠና እየታፈነ ነው አለ፡፡
95 ፐርሰንት ያህሉ አርሶ አደሮች ከብድር ተቋማት ከ5ሺ እስከ 30ሺ ብር ብድር መውሰዳቸውን ከአንድ ጥናት መረዳታቸውን የጠቆሙት የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብርሃ ደስታ፤ ዓረና ለመጪው ምርጫ የፓርቲውን ፕሮግራም ለማስተዋወቅ በተዘዋወረባቸው የገጠር ክፍሎች አርሶ አደሮቹ በወሰዱት ብድር የተነሳ  መብትና ነፃነታቸው እየታፈነ መሆኑንና ክፉኛ እንደተማረሩም ተናግረዋል፡፡
የዓረና ፓርቲ አመራሮች ህዝባዊ ስብሰባ ባደረጉባቸው ሰባት የገጠር ክፍሎች፣ የትግራይ አርሶ አደሮች በማዳበሪያ ዕዳና በብድር በመያዛቸው ህወሐትን የሚቃወሙ ከሆነና በዓረና  ስብሰባ ላይ ከተገኙ፣ ዕዳችሁን ክፈሉ እየተባሉ መውጪያ መግቢያ እንደሚያጡ አቶ አብርሃ ገልፀዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ነፃነት ተነፍገው ከህወሐት በቀር ሌላ ፓርቲ እንዳይደግፉ መብታቸውን ተነፍገዋል ብለዋል፡፡
ባለፉት  ወራት ከሳዑዲ ከተመለሱ ኢትዮጵያውያን መካከል አብዛኞቹ በትግራይ ክልል የሚገኙ ወጣቶች እንደነበሩ የጠቆሙት የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ፤ የስደት ተመላሾቹ “ለሥርዓቱ አደገኛ ናቸው” በሚል በመገለላቸው፣ አብዛኞቹ በእግርና በባህር እያቋረጡ ወደየመንና ሳኡዲ ተመልሰው እየተጓዙ ነው ብለዋል፡፡

Published in ዜና

          ለችግር የተጋለጡ ህፃናትን እና በለጋ እድሜያቸው ተደፍረው ወይም ተገደው የልጅ እናት የሆኑ ሴቶችን ለመርዳትና የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ ከሁለት ዓመታት በፊት የተቋቋመው መሠረት የበጎ አድራጎት ድርጅት በድርጅቱ የበጎ ፍቃድ አገልጋዮች ተነሳሽነት “በጎ ፍቃደኝነት” የሚል መሪ ቃል ያነገበ ልዩ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ሊያካሂድ ነው፡፡
መጋቢት 21/2006 ዓ.ም በሐርመኒ ሆቴል በሚካሄደው በዚሁ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የድርጅቱ ድጋፍ ሰጪ አካላትና ሌሎች የድርጅቱ አጋሮች እንደሚገኙበት አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
“እኛው ለእኛው በእኛው” በሚል መሪ ቃል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው ይኸው ድርጅት ምንም አይነት ቋሚ የገቢ ምንጭ ሳይኖረው ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 280 ህፃናትንና 125 ሴቶችን በመርዳት ላይ የሚገኝ ድርጅት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ህብረተሰቡ የህፃናቱን እና የሴቶችን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ያለውን በመለገስ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የድርጅቱ መስራች እና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት አዛገ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

Published in ዜና

        “ሀገሬ የህይወቴ ጥሪ” በሚል ርዕስ በ1948 ዓ.ም የተፃፈው የአቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ ግለ ታሪክ መጽሐፍ ታትሞ ለአንባቢያን የቀረበው ዘንድሮ ነው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ መጽሐፉ በተመረቀበት ወቅት ስለ ባለታሪኩና መጽሐፉ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር አህመድ ሀሰን፤ “አንድ ሰው ታሪክ ለመፃፍ ኃላፊነት አለብኝ ብሎ ከተነሳ ያልተፃፈውን ታሪክ ማሳየት መቻል አለበት” በሚል ኃይለቃል የአቶ ተስፋሚካኤል ትኩእን መጽሐፍ በማሳያነት አቅርበዋል፡፡
ባለታሪኩ ከቦታ ቦታ፣ ከአገር አገር ተንቀሳቃሽ ስለነበሩ በመጽሐፋቸው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ማየት አስችለውናል ያሉት ዶ/ር አህመድ ሃሰን፤ “ለተለያየ ጉዳይ ሲንቀሳቀሱ መልክአ ምድርን፣ ሕዝብን፣ ባህልን፣ ሥርዓትን…በትኩረት ለመመልከት ጥረዋል፡፡ የብዕር፣ የወረቀትና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት ችግር በነበረበት ዘመን የዕለት ውሎ ማስታወሻ የመፃፍ ልምዳቸው ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ ለማዘጋጀት አብቅቷቸዋል” ብለዋል፡፡
“ማንም ታሪክ ፀሐፊ ሁሉንም ሰው ሊያስማማ የሚችል የታሪክ መጽሐፍ ሊጽፍ አይችልም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ታሪክ ፀሐፊዎች ወገንተኛ ስለሚሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በ1933 ዓ.ም እንግሊዝ ኢትዮጵያን ባትረዳ ነፃነታችን ሊመለስ አይችልም ነበር የሚሉ አሉ፡፡ ያለ እንግሊዝ እርዳታ ኢትዮጵያዊያን ነፃነታቸውን ማስመለስ ይችሉ እንደነበር ከሚያምኑት አንዱ የሆኑት አቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ፣ በማስረጃነትም እንግሊዞች በከተሞች እንጂ በገጠር የነበራቸው ድርሻ አናሳ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ደራሲው እውነት ተንገዳግዳ ከወደቀችበት ብቻ ሳይሆን ሞታ ከተቀበረችበት ፈንቅላ መውጣት እንደምትችል   በመጽሐፋቸው አሳይተውናል” ብለዋል - ዶ/ር አህመድ ፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ ቤተሰባዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ትስስራቸው ከማክተሙ ትንሽ ቀደም ብሎ የአቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ ግለ ታሪክ ታትሞ ቢሆን ኖሮ፣ የልዩነት አቀንቃኞቹን በብርቱ የሚሞግት መፅሃፍ  ይሆን ነበር ሲሉ አድናቆታቸውን የገለፁት የሥነ ጽሑፍ መምህሩ መሰረት አበጀ፤ መጽሐፉ ለህትመት ከተዘጋጀ በኋላ በማማከርና በሌሎች ጉዳዮች ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን በሥራው አጋጣሚ ያዩትን ችግር ሲገልፁም “የአገራችን ትራንስፎርሜሽን የህትመት ኢንዱስትሪው ወዴትና እንዴት ማደግ እንዳለበት አቅጣጫ አለማስቀመጡ ያስገርማል” ሲሉ ተችተዋል፡፡
የመጽሐፉ አርታኢ መምህር ደረጀ ገብሬ በመጽሐፉ ውስጥ “የአርታኢው ማስታወሻ” በሚል ካቀረቡት ጽሑፍ አሳጥረው አንብበዋል። የደራሲውን ሃሳብ፣ የፃፈበትን ዘመን መንፈስና የመጽሐፉን ወጥነት ለመጠበቅ 660 የግርጌ ማስታወሻዎችን የተጠቀሙት አርታኢው፤መጽሐፉ መገረም እንደፈጠረባቸውና ጥያቄ እንዳጫረባቸው በግርጌ ማስታወሻዎቹ ገልፀዋል፡፡
አፄ ዮሐንስ ኢትዮጵያን ትልቅ አገር ለማድረግና ለማስፋፋት ልጅ ምኒልክንና ልጅ አዳልን እንዳነገሡ፣ ራስ ጐበናንም በኬንያ የማንገሥ አሳብ እንደነበራቸው፤ይህንን እቅዳቸውን የሚያውቁ ሰዎች “ለምን ልጆችዎን አያነግሱም?” ቢሏቸው “እኔን ያነገሠኝ እግዚአብሔር ነው፤ለልጆቼም እግዚአብሔር ያሰበላቸውን ይሰጣቸዋል” ማለታቸውን ደራሲው የፃፉ ሲሆን አርታኢው በበኩላቸው፤ “ይህ ሃሳብ በሌሎች መረጃዎች ይደገፍ ይሆን?” ሲሉ ጠይቀዋል - በግርጌ ማስታወሻ ላይ፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ አባት የሐማሴን ሰው መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን አርታኢው አሁንም ይጠይቃሉ፤ “የታሪክ ምርምርና የዘር ቆጠራን እንደገና መመራመር ያስፈልግ ይሆን?” በማለት፡፡
የአቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ ግለ ታሪክ መረጃ የሚሰጡ፣ መገረምን የሚፈጥሩ፣ ክርክርና ሙግት የሚያስነሱ ብዙ ታሪኮችን የያዘ መፅሃፍ ነው። መደመምን ከሚፈጥሩ ታሪኮች መካከል ከአፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ጋር ተያይዞ የተጠቀሰው አንዱ ነው፡፡
“እኔ እዘምታለሁ፤ ሱሪዎን ለእኔ ይስጡኝ ብለው እቴጌ ጣይቱ አፄ ምኒልክን ባያስጨንቋቸው ኖሮ የአድዋን ጦርነት በጣሊያን ላይ ለማንሳት ምንጊዜም ፈቃደኛ አልነበሩም” ይላል - መፅሃፉ፡፡ የዚህ ምክንያቱም አፄ ምኒልክ የትግሬን መሳፍንትና መኳንንት ይፈሩ ስለነበር ነው ብለዋል - ፀሃፊው፡፡ ከንጉሡ ፍርሃትና ከእቴጌይቱ ድፍረት ጋር በተያያዘ የተነገረ ሌላ ታሪክም አለ፡፡ “አዲስ አበባ በጭቃ የተሞላች “ፊንፊኔ” የተባለች ዱርና ገደል ነበረች፡፡ አፄ ምኒልክ በሌሉበት ከእንጦጦ ፍልውሃ ለመታጠብ ወርደው ኮረብታይቱን ለከተማነት የመረጥዋት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ናቸው፡፡ የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ግን ውራጌዎችንንና ኦሮሞዎችን ስለፈሩ ቆጥ በመሰለው የእንጦጦ ገደል ሠፈሩ”
ሊቢያ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ዘመን ኢትዮጵያዊያን ለኢጣሊያን በቅጥር ወታደርነት ማገልገላቸው፤ በገጠር ኢትዮጵያ ይተገበር የነበረውና ወላጆች ልጆቻቸውን ለማጋባት የሚስማሙበት ባህል ከእስራኤሎች የተወረሰ መሆኑን፤ ልጅ ኢያሱ ሃይማኖቱን ቀይሯል ብለው የሃሰት ወሬ በመንዛት በአገሪቱ ቀውስ እንዲፈጠር ጥረት አድርገው የተሳካላቸው የኢትዮጵያን ዕድገትና መስፋፋት የፈሩ ሦስት የውጭ አገር መንግሥታት መሆናቸውን፤ ኤርትራዊያንን የሚያሳዝን ተግባር ይፈጽሙ ስለነበሩ የአፄ ኃይለሥላሴ ባለስልጣናትና መጥፎ ሥራዎቻቸው፤ ፋሽስት ጣሊያን በተባረረ ማግስት ጠላት ትቶት የወጣውን ንብረት በሽሚያ ለመካፈልና በሃሰት አንዱ ለሌላው መስክሮ የመሿሿሙ ሂደት፤ እንግሊዝኛ ቋንቋ ማወቅ የአዋቂነት መጨረሻ ተደርጐ መወሰድ የተጀመረው ከመቼ አንስቶ እንደሆነ፤ዝሙት አዳሪነት በኢትዮጵያ የተጀመረውና የተስፋፋው እንዴትና ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ…የሚያመለክቱ ብዙ ታሪኮች በመፅሃፉ ውስጥ ተካተውበታል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው እየለፉና እየደከሙ ለስደት የሚዳረጉበት ምክንያቱ ምን እንደሆነ፣ አደገች ተመነደገች ተብሎ ሲጨበጨብላት ተመልሳ ቁልቁል የመውረድ ተደጋጋሚ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ፤ የዚህ ችግሯ ምንጭ ምን እንደሆነ፤ አድርባይነት፣ ጉቦኝነት፣ ሌላውን ጠልፎ በመጣል እራስን ከፍ ከፍ ለማድረግ መጣጣር…መነሻቸውን ሊያመለክቱ የሚችሉና ብዙ የሚያስተምሩ በርካታ መረጃዎችን የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡
 በ272 ገፆች የቀረበው “ሀገሬ የህይወቴ ጥሪ” የተሰኘው መጽሐፍ በ250 ብር ነው ለገበያ የቀረበው፡፡ አምስት ቋንቋዎችን ይናገሩ የነበሩት የመጽሐፉ ደራሲ፤ 17 መፃሕፍትን እንዳዘጋጁ የተጠቀሰ ሲሆን አስራ አንዱ በቤተሰባቸው ዘንድ እንደሚገኝና ከደራሲው ሥራዎች መካከል ታትሞ ለአንባቢያን በመሰራጨት ግለ ታሪኩ የመጀመሪያው እንደሆነ ቤተሰቦች በምረቃ ሥነስርዓቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡ መፅሃፉ ለህትመት እንዲበቃ በተለያየ መልኩ እገዛና ትብብር ያደረጉላቸውን አካላትም አመስግነዋል፡፡

Published in ጥበብ

በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር እና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትብብር የመፅሀፍ አውደርዕይ መዘጋጀቱን የደራሲያን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ገ/ክርስቶስ ሃ/ሥላሴ አስታወቁ፡፡ አውደርዕዩ ከመጋቢት 15 እስከ 21/2006 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው ቦታ ላይ እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡ በአውደ ርዕዩ ላይ መጽሐፍት በታላቅ ቅናሽ ለሽያጭ እንደሚቀርቡ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ የአውደርዕዩ መክፈቻ እለት ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በብሄራዊ ሙዚየም አዳራሽ በርካታ ደራሲያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት “በርናባስ” በተሰኘ ልብወለድ መጽሐፍ ላይ ሂሳዊ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል።

       ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ለማረሚያ ቤቶች የሚውል መፃሕፍት ማሰባሰብ ዛሬ ይጀመራል፡፡ ለቀጣዮቹ 30 ቀናት በሚቆየው የመፃሕፍት ማሰባሰብ ሥራ መጽሐፍ መለገስ የሚፈልጉ ፈቃደኞች በተመረጡ ቦታዎች እንዲያስቀምጡ በጎ ፈቃደኛዋ ጥሪ አድርጋለ ች፡፡ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ ብሄራዊ ቴአትር ጀርባ የሚገኘው ጃፋር መጽሐፍ መደብር፣ ሜጋ መጽሐፍት መደብር ቢሮ እና ፒያሳ እናት ህንፃ ፊት ለፊት የሚገኘው አብዲ መጸሐፍ መደብር መጽሐፎቹን ለማስቀመጥ የተመረጡ ቦታዎች እንደሆኑ ነርስ ሊንዳ በቀለ ገልፃለች። በ2004 ዓ.ም ብሄራዊ ቴአትር መግቢያው መጽሐፍ የሆነ ፕሮግራም አዘጋጅታ ወደ ሶስት ሺህ ያህል መጽሐፍትን በመሰብሰብ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዳስገባች የገለፀችው በጎ ፈቃደኛዋ፤ በ2005 ዓ.ም ከኅብረተሰቡ ገንዘብ በማሰባሰብ ጋሞ አካባቢ ለሚገኙ የገጠር ት/ ቤቶች የመማሪያ መጽሐፍትን በቅናሽ በመግዛት ማስረከቧን ተናግራለች፡፡ ዘንድሮም በጎ ፈቃደኞች የሚለግሷቸውን መጸሐፍት ለቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንደምታስረክብ ገልፃ፤ ሁሉም ሰው ካለው መጽሐፍ ላይ እንዲለግስ ጥሪ አቅርባለች፡፡ በጎ ፈቃደኛዋ በየዓመቱ የምታካሂደውን የመጽሐፍ ማሰባሰብ ሥራ “መጽሐፍት ለሁሉም በሁሉም ስፍራ” በሚል መርህ እንደምታከናውንም ጨምራ ገልፃለች፡፡

በደራሲ ገስጥ ተጫኔ እና በቀድሞው የኢትዮጵያ ምድር ጦር ሰራዊት ወታደሮችና ሲቪል ማህበራት ትብብር የተዘጋጀው “የቀድሞው ጦር” የተሰኘ የታሪክ መፅሐፍ ዛሬ ይመረቃል፡፡ የመጽሀፍ ምርቃቱ ዛሬ ጠዋት በዮርዳኖስ ሆቴል የሚከናወን ሲሆን 747 ገፆች እንዳሉትና በ250 ብር ለገበያ እንደቀረበ ደራሲ ገስጥ ተጫኔ ተናግረዋል፡፡ “የቀድሞው ጦር” ለደራሲው ዘጠነኛ መፅሀፋቸው ሲሆን ከዚህ በፊት “የናቅፋው ደብዳቤ”፣ “እናት አገር”፣ “የፍቅር ቃንዛ”፣ “ነበር” ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት፣ የማክዳ ንውዘትና ሌሎችንም ለአንባቢያን አድርሰዋል፡፡

በደራሲ ለማ ደገፋ የተፃፉት “ከመሩ አይቀር”፣ “ካደጉ አይቀር”፣ “ጂሩፍ ጂሬኛ” እና “የህይወት ውቅር” መፃሕፍት ዛሬ ረፋድ ላይ በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል እንደሚመረቁ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አስታወቀ፡፡ “ካደጉ አይቀር” የተሰኘው ባለ 220 ገፅ መጽሐፍ የሰውን አዕምሮ በማልማት የሚገኝ ትሩፋት ላይ የሚያተኩር ሲሆን “ከመሩ አይቀር” የአመራርን ምንነት፣ የመሪን ማንነትና የመሪ ተግባራትን በማንሳት ትንታኔ ይሰጣል ተብሏል፡፡ መጽሀፉ 145 ገፆች እንዳሉትም ታውቋል፡፡ “የህይወት ውቅር” የተሰኘው የለማ ደገፋ ሶስተኛ ተመራቂ መጽሐፍ፤ 316 ገፆች ያሉት ሲሆን ስለመንፈሳዊ ህይወት የሚገደው የትኛውም ሰው የሚማርበትና መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ የተሰናዳ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ “ጂሩፍ ጂሬኛ” የተሰኘው መጽሐፍ 367 ገፆች እንዳሉትም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Page 4 of 17