41ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በቻይናዋ ጉያንግ ከተማ  ላይ ዛሬ ሲካሄድ ባለፉት ሁለት ሻምፒዮናዎች ላይ ኢትዮጵያ በኬንያ የተወሰደባትን ብልጫ ለመመለስ ተስፋ ተደርጓል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች 24 አትሌቶችን የሚያሳትፈው የኢትዮጵያ ቡድን ባለፈው ሰኞ ምሽት ወደ ስፍራው የተጓዘ ሲሆን ከኬንያ ባሻገር ከምስራቅ አፍሪካ የኡጋንዳ፤ የኤርትራ እና የታንዛኒያ አትሌቶች እንዲሁም የአሜሪካ፤ እንግሊዝ፤ ጃፓንና የአዘጋጇ ቻይና አትሌቶች በተለያዩ የውድድር መደቦች ጠንካራ ተፎካካሪዎቻቸው እንደሚሆኑ ተዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በነበራት የውጤት ታሪክ፣ በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ማለትም በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና ታላላቅ ስኬት ያገኙ አትሌቶችን የምታፈራበት ምቹ መድረክ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ አገር አቋራጭ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዶክተር ይልማ በርታ፤ አትሌቶቹ ለሶስት ሳምንታት ጠንካራ ዝግጅት ማድረጋቸውንና በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ ካለፉት ሁለት ሻምፒዮናዎች የተሻለ ውጤት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡ አትሌቶቹ ለአንድ ወር ያህል በቀን ሁለት ጊዜ ጠንካራ ልምምድ ሲሰሩ ቆይተዋል።ኢትዮጵያ የምትገኝበት መልክኣ ምድር በከፍታ ቦታ ላይ የሚገኝ እንደሆነ የገለፁት አሰልጣኞች፤ በአንጻሩ  ውድድሩ የሚካሄድበት የቻይናዋ ከተማ ጉያንግ ዝቅተኛ ስፍራ ላይ መገኘቷ የኢትዮጵያን አትሌቶች በጠንካራ ተፎካካሪነት ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች የአየር ሁኔታውን በአግባቡ በመጠቀምና የቡድን ስራ በመስራት በነጠላም ሆነ በቡድን  አሸንፈው  ጥሩ ውጤት ይዘው እንደሚመለሱም ተስፋ አድርገዋል፡፡
በ41ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና  ላይ 51 አገራትን የወከሉ 447 አትሌቶች በአራት የአገር አቋራጭ የውድድር አይነቶች፤ በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች፣ በ8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች፣ በ8 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶችና በ12 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች ይሳተፋሉ፡፡ በሻምፒዮናው ባላቸው የውጤታማነት ታሪክ የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷዋል፡፡  የኬንያ ቡድን ምርጥ አትሌቶቹን በጉዳት ቢያጣም በከፍተኛ የበላይነት በውድድሩ ለመሳተፍ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ይበረከታል። ለ1ኛ 30ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 15ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 7ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 5ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 3ሺ ዶላር ነው፡፡ በቡድን ለሚያሸንፉ አገራት ደግሞ 60ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡
በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉት 24 አትሌቶች (12 ወንዶችና 12 ሴቶች)   በ32ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ላይ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ በመውጣት ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ተመርጠዋል፡፡ ከመካከላቸውም ከሁለት ዓመት በፊት በፖላንድ በተካሄደው 40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በግል ሜዳሊያ ካገኙት  ስድስት አትሌቶች አራቱ ይገኙበታል፡፡ በአዋቂ ወንዶች 12 ኪሎ ሜትር ኢትዮጵያን በመወከል ከፍተኛ ግምት የተሰጠው አፀዱ ፀጋዬ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት በወጣት ወንዶች የወርቅ ሜዳልያ አግኝቶ የነበረው ሐጎስ ገብረህይወትም ባለፈው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከኢትዮጵያ የተነጠቀውን የወርቅ ሜዳልያ ክብር እንዲመልስ ተጠብቋል፡፡  በአዋቂ ሴቶች የ8 ኪሎ ሜትር ውድድር ደግሞ ህይወት አያሌው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ልምድ  ያካበተችው በላይነሽ ዋቅጅራ ለተሻለ ውጤት ግምት አግኝተዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በፖላንዷ ከተማ ባይድጎስዝ ተደርጎ በነበረው  40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና  የኢትዮጵያ ቡድን በተለይ በግል ውጤት በኬንያ አቻው ከፍተኛ ብልጫ ተወስዶበት ነበር፡፡ በወቅቱ ኬንያ የአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን የሜዳሊያ ሰንጠረዥ (የግል እና የቡድን ድምር) በአምስት ወርቅ፣ ሶስት ብር እና አንድ ነሀስ በአጠቃላይ በ9 ሜዳሊያዎች አንደኛ ደረጃን በመያዝ አሸንፋዋለች፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን በ3 ወርቅ፣ በ4 ብርና በ3 ነሀስ በድምሩ በ10 ሜዳሊያዎች በሁለተኛነት ማጠናቀቁ ሲታወስ፤ በወጣት ወንዶች 8 ኪ.ሜ. የወርቅ እና ነሐስ ሜዳልያ አሸናፊዎቹ ሀጎስ ገ/ሕይወት እና ሙክታር እድሪስ፣ በአዋቂ ሴቶች 8 ኪ.ሜ. የነሐስ ሜዳልያ ባለቤቷ በላይነሽ ኦልጂራ እና በወጣት ሴቶች 6 ኪሜ. የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊዋ አለሚቱ ሀሮዬ ናቸው። በቡድን ውጤት በወጣትና አዋቂ ወንዶች የወርቅ ሜዳሊያ በወጣትና አዋቂ ሴቶች ደግሞ የብር ሜዳሊያ በማግኘት ነው፡፡
አዘጋጅነቱ ለኢትዮጵያስ?
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአይኤኤኤፍ ስር ከሚካሄዱ ፈታኝ የአትሌቲክስ ውድድሮች አንዱ ነው፡፡ መደበኛ ውድድሮቹ 4 ሲሆኑ በአዋቂ ወንዶች 12 ኪ.ሜ ሴቶች 8 ኪ.ሜ፤ እንዲሁም ለወጣቶች ወንዶች 8 ኪ.ሜ ሴቶች 6 ኪ.ሜ ይወዳደሩበታል፡፡ በ1998 እ.ኤ.አ በአዋቂዎች ምድብ በሁለቱም ፆታዎች የ4 ኪ.ሜትር አጭር ርቀት ውድድር ተጀምሮ ከ2006 እ.ኤ.አ በኋላ ተቋርጧል፡፡ ከ1973 እኤአ ጀምሮ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለ38 ጊዜያት በየዓመቱ ተካሂዷል፡፡ በእነዚህ ግዜያት በተለይ ባለፉት 25 አመታት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በየውድድር መደቡ እስከ 10 ያለውን ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ መቆጣጠራቸው ባስከተለው ጫና ሻምፒዮናው ከ2011 እ.ኤ.አ ወዲህ  በየሁለት ዓመቱ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ ሻምፒዮናው በየሁለት ዓመቱ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ 3ኛው ሲሆን በውድድሩ ታሪክ ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ የቻይናዋ ከተማ ጉያንግ የምታስተናግደው ይሆናል፡፡ በ2017 እ.ኤ.አ 42ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የኡጋንዳዋ ከተማ ካምፓላ የምታዘጋጅ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ የሻምፒዮናውን መስተንግዶ የምትጠይቅበትን ግዜ በጐረቤቷ ኡጋንዳ የተቀደመች ይመስላል፡፡  ከአፍሪካ አገራት ሞሮኮ ለሁለት ጊዜያት በ1975 እና በ1998 እኤአ፤ ደቡብ አፍሪካ በ1996 እኤአ እንዲሁም ኬንያ በ2007 እኤአ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን አስተናግደዋል፡፡ ከአውሮፓ እንግሊዝ፤ ፖላንድ፤ ፈረንሳይ፤ ስፔን ፤ፖርቱጋልና ጣልያን ከአንድ ጊዜ በላይ ውድድሩን ሲያስተናግዱ፤ አሜሪካም ከአንድ ግዜ በላይ አዘጋጅ ነበረች፤ ከኤስያ ጃፓን፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ጆርዳን ሁሉ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን አስተናግደዋል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ የምትይዘው ኢትዮጵያ ውድድሩን የማዘጋጀት እድሏ ሰፊ ይሆናል። ስለዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቢያንስ ውድድሩን በ2019 እና በ2021 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን ለማስተናገድ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነትና የኢትዮጵያ ውጤት ታሪክ
ባለፉት 40 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች የቡድን ውጤት ከቀረቡ 168 ሽልማቶች ኬንያና ኢትዮጵያ  123 በማግኘት በበላይነት ይመራሉ፡፡ በአዋቂዎች ምድብ በሁለቱም ፆታዎች በተለይ በረጅም ርቀት ኬንያ ለ35 ጊዜያት የቡድን ውጤቱን በወርቅ ሜዳልያ ስታሸንፍ ኢትዮጵያ ደግሞ ለ18 ጊዜያት የወርቅ ሜዳልያዎችን ድል አድርጋለች። የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነት ስር ከወደቀ ከ25 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በተለይ ሁለቱ አገራት ኬንያ እና ኢትዮጵያ ባሳዩት የበላይነት በየአመቱ መካሄድ የነበረበትን ሁኔታ በየሁለት ዓመት እንዲቀየር ምክንያት ሆኗል፡፡  በአዋቂ ወንዶች በአጭርና በረጅም ርቀት ከ1981 እ.ኤ.አ ወደ አሸናፊዎቹ እየተፈራረቁ የተገኙት ከኬንያና ኢትዮጵያ ነው፡፡ በታዳጊ ወንዶች ምድብም ሁለቱ አገራት ከ1982 እ.ኤ.አ ወዲህ አሸናፊነቱን ተፈራርቀውበታል፡፡ በአዋቂ ወንዶች የ12 ኪ.ሜ ውድድር ከ1986-2003 እ.ኤ.አ የኬንያ አትሌቶች ለ18 ዓመታት አከታትለው አሸንፈዋል። በአዋቂ ሴቶች ምድብም በ1994 እ.ኤ.አ የፖርቱጋል አትሌት ጣልቃ ገብታ ብታሸንፍም ከ1991 እ.ኤ.አ ጀምሮ አሸናፊዎቹ ከኬንያ እና ከኢትዮጵያ የወጡ አትሌቶች ናቸው፡፡
የኬንያው አትሌት ጆን ኑጉኒ ለ5 የተለያዩ ጊዜያት በማሸነፍ የመጀመሪያው ቢሆንም በየዓመቱ ለተከታታይ 5 ዓመታት በረጅም ርቀት ለማሸነፍ የቻለው የኬንያው ፖል ቴርጋት ነው፡፡ በአጭርና ረጅም ርቀት የአገር አቋራጭ ድርብ ድል በማስመዝገብ የመጀመሪያው አትሌት ግን ኢትዮጵያዊው ቀነኒሣ በቀለ ነው፡፡ ቀነኒሣ በአጭር ርቀት 4 ኪ.ሜ እና በረጅም ርቀት 12 ኪ.ሜ ውድድሮች በ5 ሻምፒዮናዎች በተከታታይ በማሸነፍ ብቸኛው አትሌት ሲሆን በ2008 እ.ኤ.አ ላይ በረጅም ርቀት 6ኛውን የወርቅ ሜዳልያ በማግኘቱ ደግሞ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ታሪክ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን ያስመዘገበ አትሌት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በአዋቂ ውጤታማ ከሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቶች መጠቀስ ያለባቸው ደራርቱ ቱሉና ጥሩነሽ ዲባባ ናቸው፡፡  አትሌት ደራርቱ ቱሉ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት ያሸነፈች ሲሆን፣ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በአዋቂዎች ምድብ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት እንዲሁም በአጭር ርቀት ለ1 ጊዜ ማሸነፍ የኢትዮጵያ አትሌቶችን ትልቅ ውጤት አስመዝግባለች፡፡
በአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1981 እ.ኤ.አ ላይ በአዋቂዎች ምድብ የ12 ኪ.ሜ ውድድር መሃመድ ከድር ባገኘው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ አትሌት መሐመድ ከድር ከአንድ ዓመት በኋላ በተመሳሳይ ውድድር አሸንፎ የመጀመሪያውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል፡፡ በአዋቂ ወንዶች የ12 ኪሎሜትር ውድድር ኢትዮጵያ ከሰበሰበቻቸው 10 የወርቅ ሜዳልያዎች ስድስቱን ያስመዘገበው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ ከ2002-2008 እ.ኤ.አ ባለፉት ጊዜያት ሲሆን ሌሎቹን 4 የወርቅ ሜዳልያዎች መሃመድ ከድር (በ1982 እ.ኤ.አ)፣ በቀለ ደበሌ (በ1983 እ.ኤ.አ)፣ ገብረእግዚአብሔር ገ/ማርያም (በ2009 እ.ኤ.አ) እንዲሁም ኢማና መርጋ በ2011 እ.ኤ.አ ላይ አስመዝግበዋል፡፡
በአዋቂ ሴቶች የ8 ኪ.ሜ ውድድር ደግሞ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያ የሜዳልያ የተገኘው በ1991 እ.ኤ.አ ደራርቱ ቱሉ በወሰደችው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ በ1995 እ.ኤ.አ ላይ አሁንም ደራርቱ ቱሉ የተጐናፀፈች ሲሆን ሌሎች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ደግሞ በ1975 በ2000 እ.ኤ.አ አግኝታለች፡፡ በአዋቂ ሴቶች ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው 9 የወርቅ ሜዳልያዎች 3 ከጥሩነሽ ዲባባ (በ2005፣በ2006፣ በ2008 እ.ኤ.አ) 2 በጌጤ ዋሚ (በ1996፣ በ1999 እ.ኤ.አ) እንዲሁም ወርቅነሽ ኪዳኔ (2003 እ.ኤ.አ) ተገኝተዋል፡፡
በርካታ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሜዳሊያዎችን በግል እና ከቡድን ጋር በማግኘት በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ በአጠቃላይ 27 ሜዳሊያዎችን በመውሰድ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ21 ሜዳሊያዎች መሪነቱ ላይ ተቀምጣለች።በግልና በቡድን የወርቅ ሜዳሊያዎች ድምር የአለም አገር አቋራጭን የተቆጣጠሩትም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው። በወንዶች በግል ያገኛቸውን 12 ወርቅ ሜዳሊያዎች እና በቡድን ያገኛቸውን አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ጨምሮ በ16 ወርቅ ሜዳሊያዎች ቀነኒሳ በቀለ የወንዶቹን በቁጥር አንድነት ሲይዝ፣ በሴቶችም በግሏ አምስት፣ በቡድን ዘጠኝ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ጥሩነሽ ዲባባ በ14 ወርቅ ሜዳሊያዎች የሴቶቹን ዘርፍ አንደኛነቱን ይዛለች። በአንድ የአለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቢያንስ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሰባት አትሌቶች ክብረወሰኑን ሲይዙ ሰባቱም አትሌቶች ኢትዮጵያዊያን ናቸው። እነሱም ሀይሉ መኮንን፣ ጌጤ ዋሚ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማሪያም፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰለች መልካሙ ናቸው።

 “በመስተንግዶ አጉላልተን ሳይሆን በሜዳችን ተጫውተን ማሸነፍ እንፈልጋለን” ዳዊት ፍቃዱ
በ2015 የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ካፕ እየተሳተፈ የሚገኘው የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ወደ ሁለተኛ ዙር ማጣርያ የመግባት እድሉን በሜዳው በሚያደርገው  ጨዋታ ይወስናል፡፡ ከሳምንት በኋላ የናይጄርያውን ዋሪ ዎልቭስን በመልስ ጨዋታ ባህር ዳር ላይ  የሚያስተናግደው ደደቢት ሜዳውን ተጠቅሞ በ3 ንፁህ ጎሎች ማሸነፍ ከቻለ ጥሎ ማለፍ ይችላል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመርያ ጨዋታቸው ከሳምንት በፊት ሲገናኙ ዋሪ ዎልቭስ 2ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ ደደቢት በቅድመ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሲሸልሱን ኮት ዲ ኦርን 5 ለ2 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፎ ወደ 1ኛው ዙር ያለፈ ሲሆን ወደ ሁለተኛው ዙር የማጣርያ ምእራፍ ለመግባት የመልስ ጨዋታውን በሜዳው እና በደጋፊ ፊት ማድረጉ እድሉን ሰፊ ያደርገዋል፡፡ የደደቢት ወሳኝ የአጥቂ መስመር ተሰላፊ የሆነው ዳዊት ፍቃዱ “በመስተንግዶ አጉላልተን ሳይሆን በሜዳችን ተጫውተን ማሸነፍ እንፈልጋለን” ሲል ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡
በመልሱ ጨዋታ የምንፈልገውን ያህል ጐል ለማግባት አንቸገርም የሚለው ዳዊት፤ የባህርዳር ስታድዬም ኳስ ይዞ ለመጫወት እንደሚያመች የተናገረው ዳዊት፣ የከተማው ህዝብ ለኳስ ያለው ፍቅር በጣም ስለሚያበረታታን ውጤቱን በሜዳችን ለመጨረስ ተስፋ አድርገናል ብሏል፡፡ ከሳምንት በፊት ተደርጐ በነበረው የመጀመሪያ ጨዋታ  ልምድ ያላቸው ተጨዋቾቻችን በጉዳት ባለመሰለፋቸው እና በስብስቡ ያሉት ተጨዋቾች ከነበራቸው ልምድ ማነስ ጋር ተያይዞ 2ለ0 ለመሸነፋችን ምክንያት ነበር ያለው ዳዊት፤ በመልሱ ጨዋታ ግን የተጐዱ ተጨዋቾች በሙሉ ጤንነት መመለሳቸው፤ ወጣት ተጨዋቾችም በጥሩ ሞራል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸው በሜዳችን ብልጫ አሳይተን እንድናሸንፍ የሚያግዝ ይሆናል ሲል ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡  
ከደደቢት እና ከዋሪ ዎልቭስ በመልሱ ጨዋታ ጥሎ የሚያልፈው ክለብ በሁለተኛ ዙር ማጣርያ ሊገናኝ የሚችለው ከሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ሸንዲ ወይንም ከዲሪ ኮንጎው ኤምኬ ኢታንችዬቴ አሸናፊ ጋር  ይሆናል፡፡ ሁለቱ ክለቦች ከሳምንት በፊት ባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታቸው አልሃሊ ሸንዲ 2ለ1 በሆነ ውጤት ኤምኬ ኢታንችዬቴን አሸንፎታል፡፡ የ28 ዓመቱ የደደቢትና የብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዳዊት ፍቃዱ፤ ክለቡ ዋሪ ዎልቭስን ጥሎ ካለፈ ቀጣዩ ተጋጣሚ የሱዳኑ ክለብ እንዲሆን ይመኛል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዳ ባለፉት 4 ዓመት ለደደቢት ክለብ በመሰለፍ በሰሜንና ምእራብ አፍሪካ ክለቦች ላይ 9 ጐሎችን ማግባቱን አስታውሶ፤ ከሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ሸንዲ ጋር ደደቢት በተገናኘበት ወቅት ብቻ እንዳላገባ በመጥቀስ ይህን ታሪክ ለመቀየር የሚችልበትን አጋጣሚ ስለሚፈልግ መሆኑን አብራርቷል፡፡
የዋሪ ዎልቭስ ዋና አሰልጣኝና ሌሎች የክለቡ አመራሮች ደደቢት የመልስ ጨዋታው በባህርዳር ስታድዬም ለማስተናገድ የወሰነው ጫና ለመፍጠር ነው በማለት ማማረራቸውን ከሰሞኑ ሱፕር ስፖርት ዘግቦ ነበር፡፡ የደደቢት አሰልጣኝ ዮሃንስ ተሰማ በመጀመርያው ጨዋታ ክለባቸው በምእራብ አፍሪካው ክለብ አላስፈላጊ መስተጓጎል እና የመስተንግዶ በደል መፈፀሙን በመውቀስ ለሱፕር ስፖርት አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ የተሰማ ምሬት ነበር፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ ደደቢት ወደ ናይጄርያ ሌጎስ ከተማ በቀጥታ በረራ ቢያቀናም የዋሪ ክለብ ስታድዬም ወደ የሚገኝበት ከተማ የሚደረገው በረራ ተሰርዞ ቤኒን አቋርጦ  100 ኪሎ ሜትሮች ገደማ በመኪና ተጉዞ ለመሄድ መገደዱ አይዘነጋም፡፡ ዳዊት ፍቃዱ ወደ ናይጀርያ ሲሄዱ በመኪና አድካሚ ለማድረግ መገደድ ብቻ ሳይሆን  በአየር ማረፊያው በመጉላላት፣ በምግብ እና በሌሎች ሁኔታዎች ተፅእኖ ተደርጎብን ነበር ይላል፡፡ የናይጄርያው ክለብ ዋሪ ዎልቭስ ልዑካን  ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ግን  አላስፈላጊ መጉላላት በመፍጠር ጫና ለማድረግ ማንም አይፈልግም በማለት ለስፖርት አድማስ የተናገረው ዳዊት፤ የክለቡ ልዑካን ከአዲስ አበባ በአውሮፕላን ወደ ባህርዳር እንደሚጓዙ ከዚያም ወደ ስታድዬሙ በ10 ደቂቃ እንደሚደርሱ ገልፆ ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይ በመሆናቸው በአግባቡ እንግዶቹን አስተናግደን በሜዳ ላይ በምናሳየው ብቃት የጨዋታውን ውጤት ለማግኘት እንፈልጋለን ብሏል፡፡
ደደቢት በቅድመ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሲሸልሱን ኮት ዲ ኦርን 5 ለ2 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፎ ወደ 1ኛው ዙር ያለፈ ሲሆን ወደ ሁለተኛው ዙር የማጣርያ ምእራፍ ለመግባት የመልስ ጨዋታውን በሜዳው እና በደጋፊ ፊት ማድረጉ እድሉን ሰፊ ያደርገዋል፡፡ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም በአፍሪካ ደረጃ ብቁ ተሳታፊ ለመሆን የበቃው የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ዘንድሮ በካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ ሲሳተፍ 3ኛው የውድድር ዘመን ነው፡፡ በ2011 እና በ2013 እኤአ በኮንፌደሬሽን ካፕ ሲሳተፍም  በቅድመ ማጣርያዎች ተጋጣሚዎችን ጥሎ ቢያልፍም በአንደኛ ዙር ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች  ተሰናብቷል፡፡ በ2014 እኤአ ላይ ደግሞ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያውን ቢያልፍም  አንደኛ ዙር ማጣርያውን ሳያልፍ ቀርቷል፡፡
የናይጄርያው ክለብ ዋሪ ዎልቭስ ተኩላዎቹ በሚል ቅፅል ስሙ ይታወቃል፡፡ በካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ ከዘንድሮ በፊት ለሶስት ጊዜያት ተሳትፎ የነበረው ክለቡ በ2010 እኤአ ላይ 16 ቡድኖች ውስጥ ሲገባ በ2012 እና በ2014 እኤአ  እስከ ሁለተኛ ዙር ማጣርያ ደርሷል፡፡ ዋሪ ዎልቭስ በስብስቡ  16 ናይጄርያዊ ተጨዋቾችን ያቀፈ ሲሆን ካሉት ሌሎች አራት ፕሮፌሽናሎች ጋር  አጠቃላይ የዋጋ ግምቱ 575ሺ ዩሮ ነው፡፡ የቡድኑ አማካይ እድሜ ደግሞ 27.3 አመት ነው፡፡

 በአዋቂ ወንዶች 12 ኪ.ሜ
በግል -10 ወርቅ፤ 5 ብር፤ 6 ነሐስ (14 ወርቅ፣ 15ብር፣ 14 ነሐስ)
በቡድን - 8 ወርቅ፤ 13 ብር፤ 6 ነሐስ (24 ወርቅ፣ 3ብር፣ 3 ነሐስ)
በአዋቂ ወንዶች ከ6 እስከ 8 ኪ.ሜ (ከ1998-2006 እ.ኤ.አ)
በግል - 6 ወርቅ፤ 2 ብር፤ 1 ነሐስ
በቡድን - 2 ወርቅ፤ 4 ብር፤ 3 ነሐስ
በአዋቂ ሴቶች 8 ኪ.ሜ
በግል - 9 ወርቅ፤ 8 ብር፤ 10 ነሐስ (4 ወርቅ፣ 6 ብር፣ 5 ነሐስ)
በቡድን - 10 ወርቅ፤ 11 ብር፤ 1 ነሐስ (11 ወርቅ፣ የብር፣ 2 ነሐስ)
በአዋቂ ሴቶች ከ4 እስከ 6 ኪ.ሜ (ከ1998-2006 እ.ኤ.አ)
በግል - 4 ወርቅ፤ 4 ብር፤ 2 ነሐስ
በቡድን - 10 ወርቅ፤4 ብር፤ 0 ነሐስ
በወጣት ወንዶች 8 ኪ.ሜ
በግል -13 ወርቅ፤ 7 ብር፤ 10 ነሐስ
በቡድን -  7 ወርቅ፤22 ብር፤ 0 ነሐስ
በወጣት ሴቶች 6 ኪ.ሜ
በግል - 7 ወርቅ፤ 4 ብር፤ 7 ነሐስ
በቡድን - 9 ወርቅ፤9 ብር፤ 3 ነሐስ
ምንጭ ፡- www.iaaf.org

   ናይጀሪያ በዛሬው ዕለት የምታከናውነውን ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ከቦኮ ሃራም ጥቃትና ከውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት ለመከላከል እንዲሁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ  በሚል ካለፈው ረቡዕ ምሽት ጀምሮ ሁሉንም የባህርና የየብስ ድንበሮቿን መዝጋቷን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የናይጀሪያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፓትሪክ አባ ሞሮ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የሌሎች አገር ዜጎች ድንበር አቋርጠው በመግባት በአገሪቱ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት እንዳቀዱ የሚያመለክቱ መረጃዎች በመገኘታቸው፣ ምርጫውን ከውጭ ጣልቃ ገብነቶች ለመከላከል ሲባል ድንበሮቹ ተዘግተዋል፡፡
ቦኮ ሃራም በተባለው የአገሪቱ ጽንፈኛ ቡድን ላለፉት ስድስት አመታት ሲፈጸሙ የቆዩ ጥቃቶችን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ናይጀሪያውያን፣ በዛሬው ምርጫ ድምጽ መስጠት እንደማይችሉም ዘገባው አስታውቋል፡፡
ባለፉት ስድስት ሳምንታት የአገሪቱ ሃይሎች በአሸባሪው የቦኮሃራም ቡድን ቁጥጥር ስር የነበሩ የድንበር አካባቢዎችን መልሰው መያዝ ቢችሉም፣ በተለይ በሰሜን ምስራቃዊ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰርጎ ገቦች ድንበር ጥሰው ገብተው ምርጫውን ያደናቅፋሉ በሚል ስጋት መንግስት ሁሉንም የአገሪቱ ድንበሮች ለመዝጋት መወሰኑን ዘገባው ገልጧል፡፡
ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ሲባል፣ ሁሉም የአገሪቱ ድንበሮች እስከ ዛሬ እኩለ ሌሊት ድረስ ዝግ ሆነው እንደሚቆዩና ቦኮ ሃራም በሚንቀሳቀስባቸው ቦርኖ፣ ዮቢና አዳማዋ ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደተጣለም ተዘግቧል፡፡
የቦኮ ሃራምን ጥቃት የመቋቋም ቁርጠኝነትና ብቃት ያንሳቸዋል በሚል በስፋት ሲተቹ የቆዩት ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፣ በጸጥታ ስጋት ለሳምንታት ተራዝሞ  ዛሬ በሚካሄደው ምርጫ ከተቀናቃኛቸው የቀድሞው የጦር መሪ ሙሃማዱ ቡሃሪ ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው ቢቢሲ ጠቁሟል፡፡
ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፤ ጦራቸው በቦኮ ሃራም ቁጥጥር ስር የሚገኙ የአገሪቱ ግዛቶችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ውስጥ እንደሚያደርግ ባለፈው ሳምንት ቢናገሩም፤ ቦኮ ሃራም እስከ 11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 500 ህጻናትን ዳማሳክ ከተባለችው የአገሪቱ ከተማ አፍኖ መውሰዱን ቢቢሲ ባለፈው ማክሰኞ ዘግቧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

በሽታው እስካሁን ከ10 ሺ በላይ ሰዎችን ገድሏል

    ከአንድ አመት በፊት በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተቀሰቀሰውና ከ10ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈት እንደዳረገ የተነገረለት የኢቦላ ወረርሽኝ እስከ መጪው ነሐሴ ወር ድረስ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የተመድ የኢቦላ ምላሽ ግብረ ሃይል ሃላፊ ኢስማኤል ኦውልድ ቼክን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በጊኒ የተከሰተውንና ወደ ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገራት የተስፋፋውን የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ፣ በመጀመሪያዎቹ የወረርሽኙ ወራት በተመድ የተሰሩት ስራዎች ያልተቀናጁና በእውቀት ላይ ያልተመሰረቱ ነበሩ፡፡
ይሄም ሆኖ ግን ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች በሂደት እየተሻሻሉ መጥተዋል ያሉት ሃላፊው፤ ባለፈው አንድ አመት ኢቦላን ለመግታት በተደረገው እንቅስቃሴ ልምድ ቀስመናል፤ ወረርሽኙን እስከ መጪው ነሐሴ ወር ሙሉ ለሙሉ መግታት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
የኢቦላ ቫይረስ ዳግም በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት ለመከላከልና አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ሲባል፣ ራሱን የቻለ አለማቀፍ የኢቦላ ፈጣን ምላሽ ቡድን ለማቋቋም የሚያስችል ዕቅድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መውጣቱንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
ድንበር የለሹ የሃኪሞች ቡድን በበኩሉ፤እስካለፈው ጥር ወር ድረስ በምዕራብ አፍሪካ አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም፣ ከዚያ በኋላ አልቀነሰም፤ ወረርሽኙ ገና ሙሉ ለሙሉ አልተገታም ብሏል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው፣እስከያዝነው ሳምንት መጨረሻ ድረስ፣4ሺ 296 ላይቤሪያውያን፣ 3ሺ 742 ሴራሊዮናውያን፣ 2ሺ 261 ጊኒያውያን፣ 8 ናይጀሪያውያን፣ ስድስት ማሊያውያንና አንድ አሜሪካዊ በኢቦላ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

በዓለማችን በግዙፍነቱ አቻ እንደማይገኝለት የተነገረውና ሃይብሪድ ኤር ቪሄክልስ በተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ ዲዛይን የተደረገው “ኤርላንደር 10” የተሰኘ አዲስ አይነት አውሮፕላን ከስድስት ወራት በኋላ ስራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ በእንግሊዝ ሰማይ ላይ የሙከራ በረራ እንደሚያደርግ ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
በአሜሪካ የጦር ሃይል ለወታደራዊ አሰሳ ስራ እንዲውል ታስቦ የተሰራው ይህ አውሮፕላን፤ርዝማኔው ከአንድ የእግር ኳስ ሜዳ እንደሚበልጥ የጠቆመው ዘገባው፣ 302 ጫማ ቁመት እንዳለው፣ዲዛይኑም ከተለመደው ወጣ ያለና የአውሮፕላንና የሄሊኮፕተር ቅልቅል እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ኩባንያው የአውሮፕላኑን ፕሮጀክት ከጀመረ ቆየት ቢልም፣ በበጀት እጥረት ምክንያት ሥራው  ሲጓተት መቆየቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ በመጨረሻም ከእንግሊዝ መንግስት ባገኘው የ5.1 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስራውን ከዳር ማድረሱን አስታውቋል፡፡
አውሮፕላኑ 10 ቶን ክብደት የመጫን አቅም ያለው ሲሆን አጠቃላይ አሰራሩ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ነው ተብሏል፡፡ ነዳጅ ቆጣቢነቱ፣ በአስቸጋሪ የአየር ንብረት ሁኔታዎችን ተቋቁሞ የመብረር ብቃቱና በአካባቢ ብክለት እምብዛም አለመታማቱም ተመስክሮለታል፡፡
ኤርላንደር 10 ለመነሳትና ለማረፍ ሰፊ ማኮብኮቢያና የተመቻቸ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ የሚፈልግ አለመሆኑና በቀላሉ መንቀሳቀስ በሚችልበት መልኩ መሰራቱ ደግሞ፣ ከወታደራዊ አሰሳ ባለፈ በአደጋ ጊዜ የፈጥኖ ደራሽ ስራን ለማከናወን ተመራጭ አድርጎታል ብሏል ዘገባው፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Saturday, 28 March 2015 09:21

አለመተኛት መዘዙ ብዙ ነው!

ለበሽታ ያጋልጣል፤ ለሞት ይዳርጋል
    በሥራ ቦታዬና በመኖሪያ አካባቢዬ የሚገጥሙኝ ነገሮች ሁሉ ህይወቴን በጭንቀትና በሥጋት የተሞላ ያደርጉታል፡፡ የቱንም ያህል የሚያደክም ሥራ ስሠራ ብውል የረባ ሰላማዊ እንቅልፍ አይወስደኝም፡፡ አልጋዬ ላይ ወጥቼ ስገላበጥ፣ መጽሐፍ ሣነብ፣ ቲቪ ስመለከት እቆይና … ሊነጋጋ ሲል ሸለብ ያደርገኛል፡፡ እሱም ቢሆን ፍፁም ሠላማዊ አይደለም፤ የጭንቀት እንቅልፍ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቀን ውሎዬ ላይ ትልቅ ችግር እየፈጠረብኝ ነው፡፡ በሥራ ላይ የመነጫነጭ፣ የድካምና የስልቹነት ባህርይ በማሳየቴ፣ ከአለቆቼ ዘንድ ተደጋጋሚ ተግሣፅና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል፡፡
የእንቅልፍ ማጣት ችግር እንዳለብኝና ይህም በሥራዬ ላይ ተፅዕኖ እንዳሣደረብኝ ብናገርም ማንም ሊያምነኝ አልቻለም፡፡ ለችግሬ መፍትሔ ፍለጋ በግሌ ብዙ ጥሬአለሁ፡፡ ለእንቅልፍ ማጣት ችግር መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉትን ነገሮች ሁሉ አድርጌአለሁ፡፡ መፍትሔ ግን አልሆነኝም፡፡
ከፋርማሲዎች እየገዛሁ የምወስዳቸው የእንቅልፍ መድሃኒቶች ጊዜያዊ መፍትሔ ቢሰጡኝም ከችግሬ ሙሉ በሙሉ ሊያላቅቁኝ አልቻሉም፡፡ ሰዎች “መድሃኒቱ ሌላ የጤና ችግር ስለሚያስከትልብህ በተደጋጋሚ መውሰድ የለብህም” እያሉ ሲያስፈራሩኝ ለጊዜው ተወት አድርጌዋለሁ፡፡ ግን አሁንም ከእነችግሬ ነው ያለሁት፡፡
ወጣቱ የአይቲ ባለሙያ የእንቅልፍ ማጣት ችግሩ ተደራራቢ የጤና ችግሮችን ሊያስከትልብኝ ይችላል የሚለው ስጋቱ ሌላ የእንቅልፍ እጦት እንደፈጠረበት ይናገራል፡፡ የባለሙያ ምክርና እርዳታም በእጅጉ ይፈልጋል፡፡
ብዙዎች እንደቀላል የሚያዩት የእንቅልፍ ማጣት ችግር በጊዜ መፍትሄ ካልተገኘለት እስከ ህልፈት ለሚያደርስ አደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ በየዕለቱ ከሰባት እስከ ስምንት ሰዓታትን በእንቅልፍ የሚያሣልፉ ሰዎች ንቁና ቀልጣፋ ሲሆኑ አዕምሮአቸውን በአግባቡ ለማዘዝ የሚችሉም ናቸው፡፡ በተቃራኒው በቀን ከሰባት ሰዓታት በታች የሚተኙ ሰዎች ለደም ግፊት፣ ለስኳር፣ ለልብና ለአስም ሕመሞች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ሲሆን ለድብርት፣ ለውጥረትና ለማንኮራፋት ችግሮችም የተጋለጡ እንደሚሆኑ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጠቅላላ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ፋሲል ተሾመ ይገልፃሉ፡፡ የእንቅልፍ ማጣት ችግር በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል ያሉት ሃኪሙ፤ አነቃቂ ዕፆችን መጠቀም፣ የአልኮል መጠጦችን መጠጣት፣ የዕድሜ መግፋት፣ እጅግ የበዛ ሀዘን ወይም ደስታ የችግሩ አብይ መንስኤዎች እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
ህፃናት በዕድሜ ከፍ ካሉ ሰዎች የበለጠ ጊዜ በእንቅልፍ እንደሚያሳልፉ የሚናገሩት ዶ/ር ፋሲል፤ እድሜያችን እየጨመረ በሄደ ቁጥር የእንቅልፍ ሰዓታችን ጊዜ እያነሰ ይሄዳል ብለዋል፡፡
ለእንቅልፍ ማጣት ችግር የሚታዘዙ የተለያዩ መድሃኒቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሰሚኔክስ ዶርሚን፣ ዳሰይሬይ፣ ሶናትና ሐሊሲዬን ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች የየራሳቸው የጐንዮሽ ጉዳት እንዳላቸው የጠቆሙት ባለሙያው፤ ያለ ሃኪም ትዕዛዝ ፈጽሞ ሊወስዱ እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡ መድሃኒቶቹ ያለሃኪም ማዘዣ ሊሸጡ እንደማይችሉም የጠቆሙት ዶ/ር ፋሲል፤ ይህንን የሚያደርጉ ሰዎች በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል፡፡
የእንቅልፍ ማጣት ችግር በአለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ የጤና ችግሮችን እያስከተለ ይገኛል።  በዓለማችን ከሚገኙ ዕድሜያቸው ከሃያ ዓመት በላይ ከሆኑ ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ በእንቅልፍ ማጣት ችግር እንደሚጠቃ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል፡፡ መረጃው አክሎም፤ በአሜሪካ ከእንቅልፍ ማጣት ጋር በተያያዙ ችግሮች ሳቢያ በሚደርሱ አደጋዎች  በአመት ከ23ሺ በላይ ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉና ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ የሆስፒታል እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል፡፡
በአሜሪካ ከሚደርሱ የመኪና አደጋዎች 51 በመቶ ያህሉ በእንቅልፍ ማጣት የተነሳ የሚከሰት እንደሆነ የጠቆመው መረጃው፤ የአገሪቱ ምርታማ ዜጐቿ ስር በሰደደ የእንቅልፍ ማጣት ችግር በመጠቃታቸው በዓመት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ (200 ቢ. ብር ገደማ) ኪሳራ እንደሚደርስ አስታውቋል፡፡
የእንቅልፍ ማጣት ችግር ለመቀነስ ቡና፣ እንደ ኮካ ኮላ ያሉ ለስላሳ መጠጦችንና ቸኮሌቶችን ከመጠቀም መቆጠብ፣ የአነቃቂ እፆች ተጠቃሚ ከሆኑ በፍጥነት ማቆም፣ የአልኮል መጠጦች አመሻሽ ላይ አለመውሰድ…ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም ወደ አልጋዎ ከመሄድዎ በፊት ሰውነትዎን ዘና የሚያደርግ ልብስ መልበስ እንዲሁም ከመተኛትዎ ትንሽ ቀደም ብለው ለብ ባለ ውሃ ገላዎን መታጠብ ችግሩን ለመቀነስ ይጠቅማል ተብሎ ይታመናል፡፡  

Published in ዋናው ጤና

    በኢትዮጵያ ከሚታወቁት የሴት የቅኔ መምህራት ውስጥ አንደኛዋ እማሆይ ኅሪተ ሥላሴ ደባስ ናቸው። እማሆይ ኅሪት በአሁኑ ጊዜ የታላቁ ገዳም የዲማ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሁለተኛዋ የቅኔ መምህርት ሆነው በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡
ተወልደው ያደጉት እዚያው ዲማ አካባቢ ልደታ ለማርያም ቤተመስቀል ከተባለች ቦታ ነው። የተወለዱት በ1966 ዓ.ም ሲሆን በልጅነታቸው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገብተው ነበር፡፡ በአጋጣሚ ግን በተከሠተ የዓይን ሕመም የዓይን ብርሃናቸውን ሲያጡ፤ ወላጅ አባታቸው ከዘመናዊ ትምህርት ቤት አስወጥተው ወደ ባህላዊ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ያደርጓቸዋል። እማሆይ ኅሪት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሚሰጠውን ትምህርት ተከታትለው በቅኔ መምህርነት ተመርቀዋል፡፡
ቅኔ የተማሩት እዚያው ዲማ ጊዮርጊስ ገዳም የሐዲሳትና የቅኔ መምህር ከነበሩት ከየኔታ ዘሚካኤል ዘንድ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ደብረወርቅ ማርያም ተጉዘው ከየኔታ ከብካብ ዓለማየሁ ዘንድ ቀጽለዋል፡፡ አስከትለው በቁይ ወረዳ ውስጥ ወደሚገኘው ደቦዛ ሚካኤል ተጉዘው ከእመይቴ ወለተ ሕይወት (በአሁኑ ሰዓት የአክሱም ጽዮን ማርያም የቅኔ መምህርት ከሆኑት) ዘንድ ቅኔ ተምረዋል፡፡ እንዲሁም እዚያው ደቦዛ ሚካኤል ከጨጐዴ አካባቢ ከመጡና አሁን ደብረ ማርቆስ ቅኔ ከሚያስተምሩት ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን ዳዊት ዘንድ ቅኔን ተምረው በሚገባ አመሥጥረዋል።
እማሆይ ኅሪት ደባስ ከደቦዛ ሚካኤል እንደገና ወደ ዲማ ጊዮርጊስ ተመልሰው ሐዲሳትን ተምረዋል፡፡ ሐዲሳት ከዐራቱ ጉባኤዎች (ብሉያት ሐዲሳት ሊቃውንት መነኮሳት) አንደኛው የትምህርት ክፍል ነው፡፡ ሐዲሳትን ከተማሩ በኋላ ወደ ታላቁ የቅኔ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው ወደሚያስተምሩበት ጨጐዴ ቅድስት ሐና ቅኔ ቤት በመሄድና ለሦስት ዓመታት በመማር በቅኔ መምህርነት ተመርቀውና አስመስክረው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ወደ ዲማ ጊዮርጊስ ተመልሰዋል፡፡ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮም የቅኔ መምህርት ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ከሚያስተምሩዋቸው ውስጥ አብዛኞቹ የሴት የቅኔ ተማሪዎች ሲሆኑ ከእርሳቸው ዘንድ ዳዊት የሚማሩ የሴት ተማሪዎችም ብዙዎች ናቸው፡፡
እማሆይ ኅሪት ደባስ የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም የካቲት 21 እና 22 ቀን 2007 በአዘጋጀውና በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኘው የቤተመንግሥት አዳራሽ በተከናወነው 4ኛ ዓመት ዐውደ ጥናት ላይ ሥራዎቻቸውን ከአቀረቡ ባለሙያዎች አንደኛዋ ተጋባዥ ነበሩ፡፡ እማሆይ ያቀረቡዋቸው ቅኔዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ጉባኤ ቃና
ደራሴ ድርሰት ይብል በዘደረሰ ድርሰቱ፡፡
ፍቅረ ደብረ ድማህ ልዕልት እስከመቃብር ውእቱ፡፡
ፍቺ፡- የድርሰት ደራሲ በደረሰው ድርሰት እንዲህ ይላል፡፡ የታላቋ የደብረ ድማህ ልዕልት ፍቅር እስከ መቃብር ነው፡፡
ምሥጢር - ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ለደብረ ድማህ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያላቸው ፍቅር እስከመቃብር ነው፡፡
ጉባኤ ቃና
ለዓለመዓለም ይነብር ወይሄሉ ዝክረ ስመ ጻድቅ መፍትው፡፡
እስመ ከመ ሐዲስ ይትነሣእ ኩለሄ ስመ ዚአሁ ሕያው፡፡
ፍቺ - የተወዳጁ የጻድቅ መታሰቢያ ስም ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ ልክ ሕያው የሆነው የሐዲስ ዓለማየሁ ስም ሁልጊዜ እንደሚነሣ የጻድቅ መታሰቢያ ስም ለዘለዓለም ይኖራል፡፡
ምሥጢር - የቅኔው መነሻ “ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሔሉ፡፡” የሚለው
መዝሙረ ዳዊት ሲሆን ቅኔው የጻድቅ ስም ለዘለዓለም ሲነሣ እንደሚኖር ሐዲስ ዓለማየሁም በሥራቸው ሕያው ስለሆኑ ለዘለዓለም ይታወሳሉ እንደማለት ነው፡፡
ዘአምላኪየ
ዘመነ ምሕረት ኮነ ዘመነ ሥጋዌ ቅውም፡፡
ግእዝ ወእንግሊዝኛ አንበሳ ወላሕም፡፡
አምጣነ ወፈሩ ደርገ በህየ ደብረማርቆስ ገዳም።
ፍቺ - ቋሚ የሆነው ዘመነ ሥጋዌ የምሕረት ዘመን ሆነ፡፡ በደብረ ማርቆስ ጫካ ውስጥ አንበሳና ላም በጋራ ተሰማርተዋልና፡፡
ምሥጢር - በዚህ በተሻሻለው ዘመን አንበሳና ላም የሆኑት ግእዝና እንግሊዝኛ አቻላቻ ሆነው በአንድ ጉባኤ ላይ ቀረቡ፡፡ አንበሳው ግእዝ ሲሆን በላም የተመሰለው ደግሞ እንግሊዝኛ ነው፡፡
ዋዜማ
ሕንጻ ደብረ ማርቆስ ተጋብኦ
ከመ ይባርኩ መጽኡ ወተጋብኡ ቅድምና፡፡
ምሁራን ዘኢትዮጵያ ጽንፈ ባሕር ወጣና፡፡
ምሁራነ ጊዜ ዐቢይ እምድኅረ ሰምዑ በዜና፡፡
ክብረ ተጋብኦ ማርቆስ አምሳለ ሲና፡፡
ሐዋርያ ዘርእየ በፓና፡፡
ፍቺ - የደብረ ማርቆስን የመሰብሰቢያ ሕንጻ ይመርቁ ዘንድ የኢትዮጵያ ምሁራን ከባሕር ጠረፍና ከጣና አካባቢ ጭምር አስቀድመው መጡ፣ ተሰባሰቡ፡፡ የዐቢይ ዘመን ምሁራን በዜና ከሰሙ በኋላ መጡ፡፡ የሲና አምሳያ የሆነው የማርቆስ የክብር ጉባኤ ሐዋርያው በፓና ያየው ብርሃን ነውና፡፡
ምሥጢር - ምሁራን የደብረ ማርቆስን የባህል ዐውደ ጥናት
ያደምቁ ዘንድ ከየአቅጣጫው መጡ፡፡ የዕውቀት ብርሃንም ፈነጠቁበት፡፡
አጭር መወድስ
ለነ ለነ ለሕዝበ ጉባኤ ዘቆመ፡፡
ያብጽሐነ አምላከ ጉባኤ ከመ ዩም አመ፡፡
ፍቺ፡- ለእኛ ለእኛ ለጉባኤተኞች የቆመው የጉባኤ አምላክ ልክ እንደዛሬው ሁሉ ለሚቀጥለው ዓመት ጉባኤም ያድርሰን፡፡
ምሥጢር - የጉባኤው ተሳታፊዎች ሁሉ ለሚቀጥለው የጉባኤ ዓመት ፈጣሪ እንዲያደርሳቸው መልካም ምኞት መመኘት ነው።
በዐውደ ጥናቱ ላይ ቅኔዎቻቸውን ከአቀረቡት ውስጥ መምህር ኮከበ ጽባሕ ሰውነት አንዱ ናቸው። የኮከበ ጽባሕ ቅኔዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ጉባኤቃና
አመ ወድቀ ግእዝ አረጋዊ በዘሳባውያን ፍና፡፡
ለአንሥኦቱ ትረውጽ እንታክቲ ወለተ
ምሁራን ኅሊና፡፡
ፍቺ፡- ሽማግሌው ግእዝ በሳባውያን ጐዳና ላይ በወደቀ ጊዜ፤ የምሁራን ኅሊና የሆነች ሴት ታነሣው ዘንድ ትሮጣለች፡፡
ምሥጢር - አንድ ሽማግሌ በመንገድ ላይ ሲወድቅ አንዲት ሴት ታነሣው ዘንድ እንደምትሮጥ ምሁራንም በመውደቅ ላይ ያለውን የግእዝ ቋንቋ ያነሱት ዘንድ ጥናት እያካሄዱበት ነው፡፡
2. መወድስ
በሥርዓተ አበው ቀደምት ዘሐጸንኪዮሙ፣
ለደሃራውያን ውሉድ እመ ብዙኃን ኢትዮጵያ።
እንበለ አሐቲ ድካም ወእንበለ ንስቲት ጉዕትያ።
ጀርመን ዕቅብት ዘብእስኪ መጻሕፍተ ሀብታተ ቤትኪ ተካፈለት ነያ፡፡
ወዘንተ ተመነያ፣ አዋልደ ሮሜ ወዐረብ አሀተ ገሊላ ወሰማርያ፡፡
ወእንዘ ጀርመን ትፈትነኪ ትፈትነኪ ኬንያ፡፡
ከመ ሶርያ ለገባዖን ወከመ ገባኦን ለሶርያ፡፡
ወእንተ መውዕያ ለፀር አመነፀርኪ ህብልያ፡፡
አዕዛኒነ ኢይስምዓ ወአዕይንቲነ ኢይርዓያ፡፡
እስመ ኢናፍቅር ንሕነ ዘጸላዕትነ ጉህልያ፡፡
አዕዛኒነ ኢይስምዓ ወአዕይንቲነ ኢይርዓያ፡፡
ፍቺ፡- የብዙዎች እናት የሆንሺው ኢትዮጵያ ያለምንም ድካምና ልፋት በቀደሙት አባቶች ሥርዓት ያሳደግሻቸው የኋለኞቹ ልጆች እያሉ በዕቁባትነት (በጭን ገረድነት) የተቀመጠቺው ጀርመን (የባልሽ ቅምጥ የሆነችው ጀርመን)የቤትሽን መጻሕፍት ሀብታት (ንብረቶችን) ተካፈለች፡፡
ሰማርያና የገለሊላ እህቶች የሆኑት የዐረብና የሮማ ልጆችም ሀብት የመካፈልን ነገር (መጻሕፍት መውሰድን) ተመኙ፡፡
ጀርመን ስትፈትንሽ በቅርብ ያለቺው ኬንያም ትፈትንሻለች፡፡ ሶርያ ገባዖንን፣ ገባኦን ደግሞ ሶርያን እንደምትፈትን ኬንያም ልትፈትንሽ (መጻሕፍትን ልትዘርፍሽ) ትችላለች፡፡
የጠላት ማሸነፊያ የሆነውን ዘረፋን እያየሽ ከአስተናገድሽ (እያየሽ ዝም ካልሽ) ጆሮዎቻችን አይስሙ፣ ዓይኖቻችንም አይዩ፡፡
የጠላታችንን አጥፊነት እኛ አንወድምና፡፡ ይህ ከሚሆን ጆሮዎቻችን ከመስማት፣ ዓይኖቻችን ከማየት ቢጐድሉ ይሻላል፡፡
ምሥጢር፡- ባል ሲሞት የባልን ንብረት እካፈላለሁ ብላ በቅምጥነት ልጅ የወሰደች ወይንም ያልወሰደች ሴት ዋናይቱን የቤት እመቤት እንደምትሞግታት በቅምጥነት የተመሰለቺው ጀርመንም ምንም ሳትሠራና ሳትደክም የኢትዮጵያ ሊቃውንት የጻፉዋቸውን መጻሕፍት ዘርፋ ወሰደች፡፡ የእርስዋን ተግባር ያዩ ሌሎች አገሮችም ዘረፉ፡፡ ለዘረፋ ያሰፈሰፉ ሌሎች ሀገሮችም ስለአሉ መጻሕፍትን በትጋት እንጠብቃቸው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

Published in ህብረተሰብ

ካለፈው የቀጠለ

“ተፈጥሮና በገና ባይኖሩ ፆም ምን ይውጠው ነበር?” ያሰኘኝ ገዳም

    ከእግር አጠባው ሥነ ሥርዓት በኋላ ለጸሎት ወደ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሄድ ነው ፕሮግራሙ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ከገዳሙ ሆነው ሲያዩት አንገቱን አስግጎ በማዕረግ ቆሞ በእጅ የሚነካ ይመስላል፡፡ ሲሄዱት ግን ቁልቁለቱና ዳገቱ መከራ ያሳያል፡፡ ያለመከራ ረድኤቱን ማግኘት የማይቻል ይመስላል፡፡ የባለቤቴን የወገብ በሽታዋን የቀሰቀሰ ቀጥ ያለ ዳገት አለው፡፡ አንድ ቦታ አረፍ ስንል  ባጠገባችን ያለፈ ተጓዥ ሁሉ “አይዞሽ ትንሽ ናት የቀረችሽ” እያላት ያልፋል፡፡ አንዲት ሩህሩህ ልጅ ወደ ጫካው ሄዳ አንድ ምርኩዝ ብጤ አምጥታ ሰጠቻትና መንገድ ቀጠልን፡፡ ዕውነትም ብዙም ሳንሄድ ቤተክርስቲያኑ ጋ ደረስን፡፡ ከተሳለምን በኋላ የቆሎ ተማሪዎች እንዴት እንደሚማሩ ወደ ሚታይበት ቦታ ሄድን፡፡ ሁለት መምህራን መካከል ላይ አሉ፡፡ የቆሎ ተማሪዎቹ መምህሩ እየጠቆሟቸው እየተነሱ በተሰጣቸው ርዕስ መሰረት ያንበለብሉታል። ግሩም ትዕይንት ነው፡፡ የፕሮግራሙ /መርሀ - ግብሩ/ አንዱ አካል መሆኑ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ በግርማ - ሞገስ ወደ ቆመበት አምባ ጠርዝ ላይ ሄጄ መልክዐ - ምድሩን ተመለከትኩ - እጅግ ድንቅ፣ ትንፋሽ - አስጨራሽ አረንጓዴ ገፅታ አለው፡፡ በሰማያዊ ሰማይ ተከቦ የተፈጥሮን መንፈሣዊ ኃይል ያገዝፋል፡፡ እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን በረከቱን ለአካባቢው ዛፍና ዕፅዋት የለገሠ ከመምሰሉ የተነሳ ያለውሃ ያለፀሐይ የህይወትን መጎናፀፊያ የደረበ ያስመስለዋል፡፡ ቢሆን ነው፡፡ ቅዳሴውና ትምህርቱ እንዳለቀ እኛ ቁልቁለቱን ተያያዝነው፡፡ እንዳመጣጣችን አላዳገተንም፡፡ (‘ማዳገት’ የሚለው ቃል ‘ከዳገት’ መምጣቱን ልብ ይሏል) መንገድ ወደ አለማወቅ ሲሄዱ ሩቅ ነው፤ ወደማወቅ ሲመለሱ ግን አጭርና ቀላል ነው፡፡
ማደሪያችን ሜዳው ላይ ነው፡፡ ከገዳሙ ቅፅር ካሉት ለቢሮነት በዘመናዊ ሞድ ከተሠሩት አለፍ አለፍ ብለው እንደተቆራረጠ የሸንኮራ አንጓ በእኩል ቁመት ከተሰሩት ክብ ቤቶች አካባቢ፡፡ እዚያ ግድግዳውን ትራስ እንደምናደርግ ዓይነት አመቻችተን አነጠፍን። አንዲት የመንገድ ጓደኛችን፤ ከዚህ ቀደም ደጋግማ ወደ ገዳሙ የመጣች፣ አብረን እንድንተኛ አንጥፋለች። ምንጣፋችንን በቀላሉ ከአውቶብሳችን ለማግኘት አልቻልንም፡፡ ምክንያቱም ሹፌሩም ሆነ ረዳቱ አልተገኙም፡፡ አንድ ያሳቀንና ያሳዘነን ሁኔታ ገጥሞናል። አባን “ኧረ እቃችን አውቶቡሱ ላይ  ቀረብን” አልናቸው። “ቆይ ሹፌሩን ልፈልገው” ብለው ሄዱ፡፡ ቆይተው “ረዳቱ የት እንዳለ የሚያውቅ ሰው አግኝቻለሁ፤ ትንሽ ጠብቁ” አሉን፡፡ ጠበቅን፡፡ የተባለው ሰውና አባ መጡ፡፡ ከሰውዬው ጋር ወደ አውቶብሱ ሄድን። እኛ ይከፍትልናል ብለን ስንጠብቅ እሱ አንኳኳው አውቶብሱን፡፡ ቢያንኳኳ ቢያንኳኳ፣ የሞባይል ባትሪ ቢያበራ፤ “ወይ” የሚል ጠፋ፡፡ አቶ መንግሥቱ ለማ “ወይ የሚለው አጣ ገጠመው ዝምታ” እንዳሉት ዓይነት ነው፡፡ “አውቶብሱን ለማንኳኳትማ እኛስ መች አነስን?! ቀድመን ሞክረን ነበርኮ” ተባባልን፡፡ ምን ይደረግ?
ሹፌሩ ስልክ ላይ (“እጄ ላይ” እንደሚሉት ዳያስፖራዎች) ይደወል ተባለ፡፡ አያነሳም፡፡ በኋላ እኔ “ለምን በመናገሪያው (በ speaker) አታስነግሩም? አልኩ፡፡ ያ ዘዴ ሰራ፡፡ ሹፌሩ ተገኘ፡፡ የሚገርመው ግን ረዳቱ ያንን ሁሉ ጊዜ እውስጥ ተኝቷል፡፡ አንዳንድ ሰው ታድሏል፡፡ ከልቡ ይተኛል፡፡ እኔም በከፊል ይሄ ጠባይ አለብኝ፡፡ እስር ቤት የለመድኩት ይመስለኛል፡፡ የገዳሙ ልጆች  ዕቃችንን  ተሸከሙልን፡፡ በኋላ ሳንቲም እንስጥ ብንል አብራን ያለችው ወዳጃችን “ገዳም ውስጥ ቲፕ (Tip) የለም አለችኝ፡፡ እኔ ቅር ብሎኝ ባህሉን ተቀበልኩ፡፡
ምንጣፍና ልብሳችንን ይዘን ጨረቃን ከአናት እያየን መሬት ላይ መኝታችንን ዘረጋን፡፡ ራት ብሉ ተባለ፡፡ እኔና ባለቤቴ አልሄድንም፡፡ አብራን የምትተኛው ወዳጃችን “ከቻልኩ አመጣላችኋለሁ” ብላን ሄደች፡፡ ስትመለስ የገዳሙ ግብዣ እዚያው ገበታው ላይ የሚበላ፣ ወጡም የሚጨለፍ ነው አለችን፡፡
ጋደም ጋደም እንዳልን የበገና ቅኝት ሰማሁ፡፡ ተነስቼ ወደ መድረኩ አቅራቢያ ተጠጋሁ፡፡ ሰው ጋቢና ኩታውን ለብሶ መኮዲ መስሎ ተኮልኩሏል፡፡ ነጭ በነጭ ሆኗል አገር ምድሩ፡፡ የሞባይል፣ የታብሌት፣ የካሜራ መዓት ከሰው አናት ከፍ ተደርጎ ተይዟል፡፡ መፈክር አውራጅ መስሏል ክንዱ ሁሉ፡፡ የመድረክ መሪው እባካችሁ ከኋላ ያለውን አትከልሉ” ይላል፡፡ ብዙ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ የድምፅ መሳሪያ ገጣሚዎቹ ከፍ ዝቅ ይላሉ፡፡ የፕሮግራሙ ዝርዝር ተነገረ፡፡ የበገና ድርደራ ምሥጋና ይኖራል፡፡ አጭር ዶክመንተሪ ፊልም ይኖራል። መዝሙር በመሰንቆ ይኖራል፡፡ ምሽቱ ግርማ ሞገስ እንዳለውና መንፈሣዊ ስሜት ግዘፍ-ነስቶ እንደሚቆም ታውቆኛል፡፡ የበገናው ቅኝት ገና ንዝረት ሲጀምር አየሩ መሞቅ፣ ሽቅብ ሶምሶማ መዝለል ያዘ፡፡ ልባችን አብሮ ይነዝር ጀመር፡፡ ቀን የሥራ ቢሮዎች ናቸው የተባሉት አለፍ አለፍ ተደርገው የተሰሩት ክብ መስተዋት - ቢሮ ጽ/ቤቶች አሁን መኝታ ቤት ሆነዋል፡፡ ሰዎቹ ግን እንዳይተኙ የበገናው ትርዒት ቀስቅሶ ሰቅዞ ይዞዋቸዋል። እነዚህም ሞባይላቸውን ደግነዋል፡፡ የፕሮግራም መሪው “ግርግር አትበሉ፡፡ ጥሞና ይፈልጋል በገና!” ይላል ደጋግሞ፡፡
በገና ጀመረ፡፡ እዚያው ገዳሙ ያፈራቸው በገናውያን ናቸው፡፡ ከአቅሟም ሆነ ከቁመቷ በላይ የሆነች ትንሽ ልጅ ሳትቀር እየተንጠራራች ከሌሎቹ ጋር ምቱን አስተካክላ ትጫወታለች፡፡ ጣቶቻቸው እኩል ሰምረው ይጓዛሉ - እኩል ከመንፈሳችን እመርታ ጋር ይተምማሉ። አንገታቸውን ሰበር አድርገው፣ ተመስጦዋቸወን ወደ ውስጥና ወደ አርያም እያመጠቁ ሲከይኑ ግርም የሚል ህልም ይመስላሉ፡፡ ዕድሜ - ጠገቦቹ ዛፎች ቅጠሎቻቸውን በለሆሳስ በሽብሸባ አዋጥተዋል፡፡ ወፎች በጥንቃቄ ኅብር ጠብቀው በዝቅተኛ ዜማ ያጅባሉ፡፡ አንድ ገዳም ሙሉ ሰው ኮሽ ሳያደርግ ፍቃደ - ልቦናውን ለምስጋና - ዜማው አንበርክኳል፡፡ ፀጥታ፤ ተፈጥሮ፡፡ ቦልቡና ዝማሬ እና በገና፡፡ ሁሉ ወደየውስጡ ያሰርፃል ይህ የማያሸንፈው ፆም ከወዴት ይገኛል፡፡ የሰው ልጅ ኃይሉ ጫጫታ አይደለም፡፡ የሚል አርምሞ ነው። ቀና ቢሉ ፍፁም ሰማይ፡፡ ዝቅ ቢሉ ፍፁም መሬት - በምዕመናን የተሞላ፡፡ ዙሪያውን ቢያዩ እርጭታ ያጀበው ዛፍና ጫካ፡፡ ከዚያ የሁሉም መጠቅለያ የሆነው መንፈስ!!
የበገና መምህራኑን ጨምሮ እጅግ የማረኩኝ ገዳሙ ያፈራቸው አስር በገና ተጨዋች ሴቶች ናቸው። ከሁሉም በላይ ተስፋ ማየቴ! እኛ የምናውቃቸው እንደ ዓለሙ አጋ ያሉ በገና ተጨዋቾች እንደ ድንቅ እንደ ብርቅዬ የዱር እንስሶች እያየናቸው ስንሰስትና ስንሳሳ፤ ማን ይተካቸው ይሆን ስንል፣ ዛሬ ማታ ያየሁዋቸው ሴቶች እጅግ አድርገው ስጋቴን አስወግደውልኛል። ማርከውኛል፡፡ ተስፋዬን እንደ አካባቢው አለምልመውልኛል፡፡ ሴቶችና ወጣቶች መሆናቸውም የተወሰነ ምናባዊ ጉዞ እንዳደርግ አግዞኛል፡፡ ምነው ቢሉ፣ እስከዛሬ የማውቃቸው በገና ተጨዋቾች አንድም አዋቂዎችና ጠና ጠና ያሉ ናቸው፡፡ አንድም ደግ ወንዶች ናቸው፡፡ ከዚያ የመሰጠኝ ስለሴቶች ምጥቀተ ህሊናና መንፈሳዊ ዕርገት ሳስብ የተሻለ ሽቅብ የመመንጠው ክህሎት ያላቸው ይመስለኛል። ስስነት ለምጥቀተ - ህሊና (Transcendence of Consciousness) ቅርብ ነው ባይ ነኝ፡፡ ጸሎትና ምህላ ስስን ስሜት ከጠንካራ ስሜት ይልቅ በፍጥነት ከፍ እንዲልና የመንፈስ ማማ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፡፡
ከበገናው መንፈሳዊ ንዝረት በስተቀር ዝር የሚል ድምፅ የለም፡፡ አንዳች የሚያቅፍ መንፈሳዊ ሙቀት አለ። የበገናው ምት አረፍ ሲል ያለው ጸጥታ ይገርማል፡፡ የሚከተለውን ግጥም ያስፃፈኝ ያ ፀጥታ ነው፡፡
ፀጥታ ነው ፀጥ በሉ
የዓለም ድምፃችሁን ክሉ!
በዛፍ ጥላ ተጠለሉ፣ በፀጥታ ተከለሉ
አርምሞ ጉያ ግቡ፣
ፀጥታኮ ድምፅ አለው፣ ላንተ ብቻ የሚሰማ
እገዛ ውስጥህ የሚጮህ፣ እራስህ ውስጥ’ ሚሰማ
ላዕላይ የህይወት ትርጉም፣ የለሆሣሥ መንፈስ ማማ፡፡
በተመስጦ ሞገድ ብቻ፣
የሚያጎንህ መቀነቻ፣
የፀሎት የምህላ አቻ
ወደ አርያም መመንጠቂያ
ከምድረ ዓለም መለያያ
ፀጥታኮ ድምፅ አለው፣ ራስን ከራስ ማስታረቂያ!!
አንድ ነገር አስታወስኩ፡፡ የቺፕ ሳይዷ ዲዳ ሚስት በተሰኘው (The Dumb Wife of Cheapside) ዱሮ በዕደ ማርያም ት/ቤት ሳለን በእንግሊዝኛ የሰራነው ቴያትር ላይ አንደበቷ የተከፈተላት ዲዳ ሚስቱ እየለፈለፈች ስላስቸገረችው ጆሮው እንዲደነቁር የተደረገው መሪው ገጸ-ባህሪ የመጨረሻ ቃል፡-
“Thanks God All is Silent!” የሚል ነበር። አምላክ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ሁሉም ፀጥታ ነው እንደማለት ነው፡፡ (የዶክተሩን ሂሳብ ሳይከፍለው ጆሮው ደንቁሮ ነው) እኔም ያንን የደገምኩ መሰለኝ፡፡
በበገናውና በመሰንቆ ዝማሬው መካከል በቀረበው ዶኩመንተሪ ፊልም የረዥም ዕድሜ ባለቤት የሆነው የእየሱስ ገዳም አመሰራረት የአቡነመልከ ፄዴቅ ታሪክ፣ የገዳሙ የቅኔ ትምህርት፣ የአቋቋም፣ የዝማሬ፣ የድጓ ሥርወ - አመጣጥ በቅጡና በጥሩ ሁኔታ ተብራርቷል። ከአዲስ አበባ ሁለት መቶ አርባ ኪሎ ሜትር ላይ እንዲህ ያለ በመንፈስ የተሞላ ገዳም አለ ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡ 1200 ዓመቱን የያዘ አንጋፋ ገዳም ነው፡፡ 120 የገዳሙ ተማሪዎች አሉ፡፡
*          *         *
በገናው እኩለ ሌሊት ገደማ አበቃ! ወደ መኝታዬ ስመለስ አባ ትልቅ ኮምፎርት ሰጥተውናል ለካ! የፈራነው ብርድ ተሸንፏል፡፡ ጨረቃ በእኛ መሞቅ ተደስታ ትስቃለች፡፡
ወደ ደብረዘይት እኩለ - ፆም ፊታችንን አዙረን ለጥ አልን፡፡
*       *       *
ንጋት ላይ ቅዳሴው ይሰማል፡፡ እስከታቦቱ መውጫ ሁሉም በየፊናው ተመስጦ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሰዓቱ ደረሰ፡፡ ደውል ተደወለ፡፡ ጥሩምባ ተነፋ፡፡ እንደ ጥይት ያለ የሚጮህ ድምፅ ተሰማ፡፡
“ተኩስ ነው እንዴ?” አለች ባለቤቴ፡፡
“ይመስላል፡፡ ለታቦቱ መውጣት የደስደስ ይሆን?”
እንደገና ደወል ተደወለ፡፡ ጥሩምባ ተነፋ፡፡ ያ ተኩስም ተደገመ፡፡
በኋላ ስናጣራ ጅራፍ ነው ለካ! እንዴት ቢወነጭፉት ነው እንደጠመንጃ የሚጮኸው? ብቻ ደወሉም፣ ጥሩምባውም፣ ጅራፉም ፀጥታውን ሰንጥቆ አንዳች የድምፅ መብረቅ ፈጥሯል፡፡
ታቦቱ ወጣ፡፡ የሚያጅቡት የማታዎቹ ባለበገናዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ በበገና የሚነግሥ ታቦት አይቼ ስለማላውቅ እጅግ ስሜቴን ሰቅዞ ይዞኛል፡፡ እዚህ የታደለ ገዳም ውስጥ የያሬድ ጥበብ ታቦት ያነግሣል! ታቦቱ ዑደት ያደርጋል፡፡ ጥበቡም አብሮት ዑደት ያደርጋል!! ድምቀቱ የማይለካ ነው፡፡ የደበበ ሰይፉ ግጥም ቅኝት ትዝ አለኝ፡-
“ጊዜ በጊዜ ቀለበት -
   ሰተት፡፡”
የሚለው፡፡ በሱ ቅኝት እንዲህ አልኩ፡-
ጥበብ በመንፈስ ቀለበት -
ሰተት፡፡”
ጥበብ በመንፈሱ ዑደት  -
             ፍክት
ፀጥታው በበዓሉ ድምቀት -
               ፍንክት!
ያሬድ በጊዜ ቀለበት -
          ግብት፡፡
በየቦታችን ታደምን፡፡ ታቦቱ ዑደቱን አብቅቶ ደጃፉ መድረክ ላይ ቆመ፡፡ አንድ አባት ትምህርት ሰጡ፡፡ የመድረክ መሪው ከአሮጌው ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት በመሰራት ላይ ያለውን አዲስ ህንፃ አስመልክቶ በስለት መልክ በአዲስ እርዳታ መልክ፣ አሁኑኑ ስሜታቸው ተቀስቀሶ፣ መዋጮ ሊያደርጉ የሚሹ ካሉ፣ መድረኩ ክፍት መሆኑን ገለጡ፡፡ መዋጮ ተዥጎደጎደ፡፡ በሁለት አውቶብስ ከናዝሬት ድረስ የመጡ አማንያን ከፍተኛ የሲሚንቶ መዋጮ አደረጉ፡፡ ታላቅ የምሥራች! “የሲሚንቶ ዘመቻ” የሚል ሎተሪ ካርድ ከ10 ብር እስከ 240 ብር ይሸጣል፡፡ (10፣30፣120፣240) የምሁር እየሱስ ገዳም አበምኔት ረዥም ሰበካ አደረጉ፡፡ ካሉት ነገር ያስገረመኝ “አቡነ መልከ ፄዴቅ በመጨረሻ ንግግራቸው “እባካችሁ ከዚህ ገዳም አትቅሩ ብለው ነበር የሞቱት ሞታቸው ታውቋቸዋል” ያሉት ነው፡፡
ፕሮግራሙ የሚዘጋው በበገና ባለሙያው በመምህር ሲሳይ ምሥጋና ዜማ እንደሚሆን አሳወቁ፡፡ ሆነ፡፡
ቀጥሎ ገዳሙ ያዘጋጀልን ምሳ በአዳራሹ ሆነ። እኛ ባዳራሹ የጓሮ በር በኩል ነው ውሃ ልኩ ላይ የተቀመጥነው፡፡ ጓሮ ጓሮ ነውና የራሱ ትርዒት አለው። (ፍቅር እስከ መቃብር ላይ ወ/ሮ ጥሩዓይነት የፍቅር በር እንዳላቸው ያስታውሷል) የገዳሙ ነዋሪዎች ሽልጦአቸውን የሚቀበሉት በዚህ በር በኩል ነው፡፡ ሽልጧቸው እንዴት አባቱ ጥፍጥና እንዳለው ልነግራችሁ አልችልም - ቀምሼዋለሁ!! ሌላው እንዳጋጣሚ በጓሮው በር በኩል እኛን ያደለን ነገር ዳቤ ነው፡፡ ከቤተክርስቲያኑ መውጫ በር አካባቢ በኋላ ብዙ ሰው ተሰልፎለት ያየነውን ዳቤ እዚህ እጅ በእጅ አገኘነው አቤት ሲጣፍጥ!! ጣና ገዳም ያገኘሁዋቸው መነኩሴ፤ “ፈረንጅ የዳቤን የተመጣጠነ የምግብ አቅም ቢያጠናው ጥሩ ነበር” ስላቸው፤
“መንፈሱንስ ከየት ያመጣዋል?” ያሉኝ ነው ትዝ ያለኝ፡፡ ከምሣ በኋላ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ነው፡፡ ወልቂጤ ላይ ለሻይ አረፍ አልን፡፡
ሻይ የፈለገ ሻይ፣ ቡና ያሻ ቡና፣ ቢራ የከጀለ ቢራ ጠጣና ወደ አገራችን ጉዞ ሆነ፡፡ ደሞ ወደ ትርምሱ፣ ደሞ ወደ ሰልቺው ህይወት፣ ደሞ ወደ ሁካታና ትርምሱ ልንገባ ነው፡፡
ኦቴሎ ከመርከብ ጉዞው በኋላ ወደ ዴዝዴሞና ሲመጣ “ከዚያ ሁሉ የባህር ነውጥ፣ ከዚያ ሁሉ ማዕበል በኋላ እንዳንቺ ያለ ሰላም የሚገኝ ከሆነ ሺ ዓመት ጦርነት ውስጥ ልሁን!” ይላል፡፡ የኛ ደግሞ ግልባጩ ነው - “ከዚያ ሁሉ የመንፈስ ፀጥታ፣ ከዚያ ሁሉ የአርምሞ ትፍስህት በኋላ እንደ አዲሰሳባ ያለ ትርምስ ውስጥ ከምንገባ ምነው እዚያው የፀጥታ ውቂያኖስ ውስጥ ሰምጠን በቀረን” ያሰኛል፡፡
በዓለም  ጤና አካባቢ ስንደርስ፣  ከአውቶብሱ ከኋላ አካባቢ የተቀመጡ ወጣቶች፤ መዘመር ጀመሩ፡፡ እኔና ባለቤቴ፤
“ምነው ከወልቂጤ በጀመሩት? ተባብለናል፡
“ብዙ ሰው ሊወርድ ስለሆነ ፀሎት አድርገን እንለያይ” አለ አንድ ነጭ በነጭ የሀገር ልብስ ያደረገ ወጣት፡፡ ሁሉም ተስማማ!
አውቶብሱ ቆመ! ሁላችንም ተነስተን ፀሎት አደረስን፡፡
ወደ አዲሳባ ከመግባታችን በፊት ማህተም አረግን ማለት ነው (Rubber – stamp ማድረግ እንዲል ፈረንጅ)
እኔም የፅሁፌን (Rubber – stamp) እዚሁ አደረግሁ!

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 28 March 2015 09:16

ገንዘቡ ያለው ከታች ነው!

ጥድፍ ጥድፍ የሚሉ እግሮች፣ ቅልጥፍጥፍ የሚሉ እጆች፤
ቁርጥ ቁርጥ የሚሉ ትንፋሾች፣ እዚህና እዚያ የሚያማትሩ አይኖች፤

ጋዜጠኛው በወ/ሮ ውቢት ሁኔታ እጅግ ተገርሟል፡፡ የድምፅ መቅረጫውን እያስተካከለ ወ/ሮ ውቢትን አሁንም አሁንም ያያታል፡፡ ወ/ሮ ውቢት ተወልዳ ያደገችው እዚሁ ምስራቅ ጎጃም ደብረ ማርቆስ ከተማ እንደሆነ አስቀድሞ አውቋል፡፡ የዕድሜዋ ነገር ግን ቸግሮታል፤ “መቼም ዕድሜዋ ከ40-45 ዓመት ሳይሆን አይቀርም፣” የሚል ግምት ለራሱ ሰጠ፡፡ ሆኖም ግን በሰውነቷ ቀልጣፋነት በጣም ተደንቋል፡፡ ወ/ሮ ውቢት ከእንጀራ መጋገር ጀምሮ እስከ ማሸግና በመኪና መጫን ድረስ ያሉትን የስራ ሂደቶች ሁሉ የምትከታተለው በጣም በፍጥነት ነው። ወ/ሮ ውቢትን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ላያት ሰው፣ “እረፍት የሌላት ንብ” ትመስላለች፡፡
ጋዜጠኛውን ሌላው በጣም የገረመው ነገር፣ ወ/ሮ ውቢት ሰራተኞቿን በሙሉ የምትጠራው በቁልምጫ መሆኑ ነው፤ ሚስጥሩን ለማወቅ ጓጓ፡፡ ከሚያያቸው ነገሮች በመነሳትም ብዙ ጥያቄዎችን ማስታዎሻ ደብተሩ ላይ መመዝገብ ጀመረ፡፡ ጥያቄውን ፅፎ ቀና ሲል ወ/ሮ ውቢት በችኮላ እሱ ወደተቀመጠበት ቢሮ ስትመጣ ተመለከተ፡፡
“እሺ ወ/ሮ ውቢት ትንሽ ፋታ ካገኘሽ አሁን ቃለ መጠይቁን ማድረግ እንችላለን?” አለ   ጋዜጠኛው ማስታዎሻ ደብተሩን እየዘጋ፡፡
 “ይቅርታ ልጠይቅህ ነው የመጣሁት፤ እየጨረስኩ ነው፤ትንሽ አንድ 20 ደቂቃ ስጠኝ፤ መኪኖቹን ሸኝቼ እመጣለሁ፤” ብላው ወ/ሮ ውቢት ተመልሳ ሄደች፡፡
“እረ ምንም ችግር የለም ወ/ሮ ውቢት ጨርሰሽ ነይ፤ እኔ እንደሆንኩ ስራ አልፈታሁም፤ ስራችሁን ከርቀት ሆኜ እየተከታተልኩ ነው።” አለ ጋዜጠኛው፣ በልቡ (20 ደቂቃ! 20 ደቂቃ ደግሞ ምናላት! ቀኑን ሙሉ የሚገትሩን እንዳሉ ባወቅሽ፤) እያለ፡፡
ጋዜጠኛው የወ/ሮ ውቢትን ጨዋነትና ሰው አክባሪነቷን አደነቀ፡፡ በጣም የገረመው ነገር ግን ለቃለ መጠይቅ አለመጨናነቋ ነው፡፡ “በጣም ብዙ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጌያለሁ፡፡ ሁሉም ግን ጋዜጠኛን የሚፈሩና ለቃለ መጠይቅም በጣም የሚጨናነቁ ሲሆኑ፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ የሚናገሩትን ነገር ሁሉ በቃላቸው እስከ ማጥናት የሚደርሱ አሉ፡፡ የወ/ሮ ውቢት ግን እጅግ የተለየ ነው፡፡” አለና ለራሱ፣ ሰዓቱን ሲመለከት የተባለው 20 ደቂቃ እያለቀ ነው፡፡ የመጨረሻ ዝግጅቱን እያደረገ ሳለም ወ/ሮ ውቢት ወደ እሱ እየመጣች መሆኑን ተመለከተ፡፡
“ይቅርታ እንግዲህ የስራ ሰዓት ሆነና ደጅ አስጠናሁህ፤” አለች ወ/ሮ ውቢት የቢሮዋ ወንበር ላይ እየተቀመጠች፡፡
“እረ ምንም አይደለም ወ/ሮ ውቢት፣ እንዲያውም የስራችሁን ሁኔታ እያየሁ መቆየቴ ብዙ ጥያቄዎችን እንዳስብ አድርጎኛል፡፡”
“ዛሬ መላቀቅ የለም በለኛ!”
“እንደዛ ነው እንግዲህ ወ/ሮ ውቢት፤” አለ ጋዜጠኛው፣ በልቡ (ወ/ሮ ውቢት ስራ ብቻ ሳይሆን ቀልድ አዋቂና በራሷም የምትተማመን ሴት ናት፤) እያለ፡፡
“አይ ይሁን እንግዲህ፤ አሁን መጀመር እንችላለን፡፡” አለች ወ/ሮ ውቢት፡፡
“ስራ እንዴት ነው ወ/ሮ ውቢት?” አለ ጋዜጠኛው የድምፅ መቅረጫውን እያበራና የማስታዎሻ ደብተሩን እየከፈተ፡፡
“ስራ ጥሩ ነው፤ ከዕለት ወደ ዕለትም ስራችን እየሰፋና ብዙ ደንበኞችንም እያገኘን ነው፡፡”
“ወ/ሮ ውቢትን እንዲህ ፊትለፊት ሳያት በስራዋ ደስተኛ፣ ጤነኛና በራሷም መተማመን ያላት ሴት ትመስላለች፤ እውነት ነው?”
“እውነት ነው!” ብላ ጀመረች ወ/ሮ ውቢት ፈገግ እያለች፡፡ “እውነት ነው! በምሰራው ስራ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ሁልጊዜ የማስበው፣ ስራው እንዴት አሁን ካለበት ደረጃ ወደሚቀጥለው ከፍተኛ ደረጃ እንደሚደርስ ነው። ስራው ተስፋፍቶ ተጨማሪ ሰራተኞች መቀጠር፣ ተጨማሪ መኪኖችም መገዛት አለባቸው፡፡ በምሰራው ስራ በጣም ደስተኛ ስለሆንኩ ነው መሰለኝ ጤንነቴም ተስተጓጉሎ አያውቅም፡፡”
ወ/ሮ ውቢት ስትናገር አትጨነቅም፤ የምታወራው ከጋዜጠኛ ፊት ሳይሆን ልክ ከአንድ የቅርብ ባልንጀራዋ ጋር የምታወራ ነው የምትመስለው፡፡
“እንጀራ ሲጭኑ የነበሩት መኪኖች ያንቺ ናቸው?” ጋዜጠኛው ጠየቀ፡፡
“አንደኛው በድርጅታችን ሀብት የገዛነው መኪና ሲሆን፤ ሌላኛውን ግን ተከራይተነው ነው፡፡ በቅርቡ ግን የራሳችንን ተጨማሪ መኪና እንገዛለን፡፡”
ጋዜጠኛው ተገረመ! ‘እንጀራ በመሸጥ ይሄንን ያህል ደረጃ ይደረሳል’ የሚል ሃሳብ እንኳን በእውኑ በህልሙም አስቦት አያውቅም፡፡ ብዙ ሰው እንጀራ መሸጥ ከኑሮ ችግር የተነሳ የሚሰሩት ስራ እንደሆነ ስለሚያስብ፣ በእንጀራ መሸጥ ለሚተዳደር ሰው ከንፈሩን ይመጣል እንጂ እንደዚህ ትልቅ የሀብት ምንጭ ይሆናል ብሎ የሚያስብ የለም፡፡
“ወ/ሮ ውቢት አሁን ስንት ሰራተኞች አሉሽ?”
“ባጠቃላይ ዘጠኝ ሰራተኞች አሉኝ፤ ሁለት ጥበቃዎች፣ አምስት እንጀራ ጋጋሪዎችና ሁለት ሹፌሮች፡፡ ሁሉም ታዲያ ስራ ወዳድና በጠባያቸውም የተመሰገኑ ናቸው። እንጀራ ጋጋሪዎቹ ወደኔ ድርጅት ከመምጣታቸው በፊት ወላጆቻቸውን በቤት ውስጥ ስራ ከመርዳት ውጭ ምንም ዓይነት ሌላ ገቢ የሚያገኙበት ስራ ያልነበራቸው ናቸው፡፡ አሁን በወር ጥሩ ደምወዝ እከፍላቸዋለሁ፡፡ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውንም በመርዳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ስራው የበለጠ ሲስፋፋ ደግሞ ልክ እንደነዚህ ዓይነት ተጨማሪ ሰራተኞችን እንቀጥራለን፡፡”
“ቅድም ስራችሁን ስከታተል አንድ የገረመኝ ነገር ነበር፤ ሰራተኞችሽን የምትጠሪያቸው በቁልምጫ ነው። ለምንድነው? በአሰሪና ሰራተኛ መካከል እንደዚህ ዓይነት ነገር ብዙም የተለመደ ነገር አይደለም ብዬ ነው፡፡
 “ስለምወዳቸው እኮ ነው! በባህሪያቸውና በስራቸው በጣም ያስደስቱኛል፡፡ በርግጥ ሰራተኛን የማቅረብና እንደዚህ በቁልምጫ የማቅረብ ነገር በባህላችን እምብዛም የተለመደ ነገር አይደለም። አሰሪ ሁልጊዜ የሚቆጣ፣ ደምወዝ የሚቀጣና ከስራ የሚያባርር ስለሆነ በሰራተኞቹ ዘንድ የተፈራ ነው፡፡ ጥያቄው ግን፣ ስራ መሰራት ያለበት በዚህ መንገድ ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡ በዚህ መንገድ ስራ ሊሰራ ቢችልም፣ አስደሳችና ውጤታማ ሊሆን ግን አይችልም፡፡ ሰራተኛው በስራው እየተደሰተ አብሮ ከድርጅቱ ጋር ማደግ አለበት እንጂ ድርጅቱ ከሰራተኞቹ ተነጥሎ ሊያድግ አይችልም፡፡ እኔ አነሱን እያስከፋሁና እያሳቀኩ የማገኘው ገንዘብ አያስደስተኝም፡፡ ሰራተኞቼን የማቆላምጣቸው በእኔና በእነሱ መካከል ክፍተት እንዳይፈጠርና በመካከላችን መግባባት፣ መቀራረብና መዋሀድ ስለሚያመጣ ነው፡፡”
ጋዜጠኛው በወ/ሮ ውቢት ንግግር ፈዟል። ማስታዎሻ መያዙን ትቶ በጥሞና ያዳምጣታል። የቱን ፅፎ የቱን ይተወዋል፤ ድምፅ መቅረጫው ይጨነቅበት፡፡ ወ/ሮ ውቢት ንግግሯ ውበት ያለውና የሚያሳምን ነው፡፡
“ወ/ሮ ውቢት ስንት ልጆች አሉሽ? የባለቤትሽና የልጆችሽስ ሚና በስራሽ ላይ ያለው አስተዋፅዖ መንድነው?”
“ሦስት ልጆች አሉኝ፤ የመጀመሪያዋ ልጄ የዩነቨርሲቲ ተማሪ ስለሆነች አሁን ከአጠገቤ የለችም፡፡ ሁለቱ ልጆቼ ግን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሲሆኑ በስራዬ ውስጥ ሁልጊዜ አብረውኝ አሉ፡፡ ተማሪዎች ስለሆኑ ግን ሙሉ በሙሉ በዚህ ስራ ውስጥ እንዲገቡ አልፈቅድላቸውም፡፡ በተረፈ የባለቤቴ እገዛ ግን ተነግሮ አያልቅም፡፡ እኔና ባለቤቴ አንድ መ/ቤት ውስጥ አብረን ነበር የምንሰራው፡፡ የቢሮ ስራዬን ትቼ ወደዚህኛው የግል ስራ የገባሁት ከባለቤቴ ጋር ተነጋግረንና ወስነን ነው፡፡ እኔ እንጀራውን እየጋገርኩ የማቀርብበትን ሆቴል ያገኘልኝም ሆነ ለስራዬ መነሻ የሚሆን ገንዘብ ከመ/ቤቱ ተበድሮ የሰጠኝ ባለቤቴ ነው፡፡ ባጠቃላይ ልጆቼም ሆኑ ባለቤቴ ከእኔ ስራ ጋር በአንድ ቅኝት ውስጥ በመጓዛችን ነው ዛሬ ለዚህ ደረጃ የበቃነው፡፡”


ከቢሮ ስራ ወደ እንጀራ ጋጋሪነት! ጋዜጠኛው በጣም ተደነቀ፡፡ ይሄ በህብረተሰባችን ወስጥ እንግዳ የሆነና እንደ እብደትም የሚቆጠር ውሳኔ ነው፡፡ ጋዜጠኛው ከዚህ የወ/ሮ ውቢት ውሳኔ ጀርባ ያለውን ውጣ ውረዷንና ቆራጥነቷን ማወቅ ፈለገና ሌላ ጥያቄ አነሳ፣
“ከባድ ውሳኔ ይመስለኛል ወ/ሮ ውቢት! የቢሮ ስራ ትቶ በእንጀራ ጋጋሪነት ለመሰማራት መወሰን በኛ ማህበረሰብ ውስጥ ከባድ ነው፤ ትልቅ ቁርጠኝነትና በራስ መተማመንን ይጠይቃል፡፡ በዚህ በኩል የስራ ባልደረቦችሽን አማክረሽ ነበር? ምን አሉሽ?”
“ቢሮ ውስጥ አብረውኝ የሚሰሩ ጓደኞቼን አማክሬያቸው ነበር፡፡ ቃል በቃል ‘ይሄ እብደት ነው!’ ነበር ያሉኝ፡፡ ‘ሰው እንዴት የተከበረ የቢሮ ስራውን ትቶ ልክ እንደ ችግረኛ አመድ ለአመድ ልርመጥመት ይላል፤ ምን ቸግሮሽ ነው እንጀራ ሸጬ ልኑር የምትይው!’ ብለው በጣም ተቆጡኝ፡፡ እኔ ግን የስራውን አዋጪነት ቀደም ብዬ ከባለቤቴ ጋር በደንብ አይተነዋል፡፡ ደግሞም ከድሮ ጀምሮ በውስጤ የሆነ ነገር ነበር፤ ይሄውም የራሴን የግል ስራ እየሰራሁ በእሱ ማደግን ከድሮ ጀምሮ የምመኘው ነገር ነው፡፡ እናም እስከዚያ ቀን ድረስ ውጤታማ የምሆንበትን ስራ እያጠናሁ ነው የቆየሁት፡፡ በአንድ ነገር ላይ ካመንኩበት ደግሞ የሚያቆመኝ ነገር የለም፡፡ ያንን ነገር ካላሳካሁት እረፍት የለኝም፤ ነጋ ጠባ ውስጤ ተሰንቅሮ ይነዘንዘኛል። ይሄ እንግዲህ የግል ባህሪዬ ነው፡፡ ጓደኞቼ ከውስጥ የሚነዘንዘኝን ነገር አያውቁትም፡፡ እነሱ ነገሮችን የሚያዩት ከራሳቸውና ከማህበረሰቡ አስተሳሰብ አንፃር ነው፤ ለዚህም ነው፣ ‘እብደት ነው!’ ያሉኝ፡፡
ጋዜጠኛው ወ/ሮ ውቢት የቢሮ ስራዋን ከመልቀቋ በፊት የነበረባትን የሃሳብ ሙግት በአይነ ህሊናው መቃኘት ጀመረ። እውነትም ከባድ ውሳኔ ነው! ወ/ሮ ውቢት ከዚህ የሀሳብ ሙግት በኋላ በስተመጨረሻ ወደ ተግባር የተሸጋገረችበትን ቅፅበት ለማወቅ ጓጓና ሌላ ጥያቄ አስከተለ፣
“እና በስተመጨረሻ የቢሮ ስራሽን ለቀሽ ወደ እንጀራ መጋገር ስራሽ እንድትገቢ ያስቻለሽ ቅፅበት ምንድን ነበር?”
“በእንደዚህ አይነት የሃሳብ ሙግት ላይ እያለሁ ድሮ የማውቃት አንድ ጓደኛዬን በአጋጣሚ መንገድ ላይ አገኘኋትና ስለኑሮና ቤተሰብ ማውራት ጀመርን፡፡ እሷ አሁን በምትኖርበት አካባቢ በጥቃቅንና አነስተኛ ነጋዴነት ተደራጅታ እየሰራች እንደሆነና ጥሩ ገቢም እንዳላት ነገረችኝ። እኔም የቢሮ ሰራተኛ መሆኔንና ሆኖም ግን ስራዬን ለቅቄ እንጀራ በመጋገር ለተለያዩ ሆቴሎች በማስረከብ ስራ ላይ ለመሰማራት ማሰቤን ነገርኳት፡፡ ከባለቤቴ ቀጥላ ይሄንን ሃሳቤን የደገፈችው ብቸኛዋ ሰው ይቺ የድሮ ጓደኛዬ ናት፡፡ ከምክሮቿ ውስጥ ሁሉ ግን ውስጤን ያቀጣጠለውና ሁልጊዜም ከውስጤ የማልረሳው አንድ ነገር አለችኝ፣ “አትሞኝ! ሰው ሁሉ ጨዋታው ያለው ከላይ ይመስለዋል፤ አይደለም፡፡ ገንዘቡ ያለው ከታች ነው!” ይሄ አነጋገሯ በቋፍ ላይ የነበረውን ሃሳቤን እንዲለይለት አደረገኝ፡፡ ውስጤ በጣም ተቀጣጠለ! በነጋታው የቢሮ ስራዬን ለቀኩ፡፡ ከዚያም አንድ እንጀራ ጋጋሪ ቀጠርኩና ስራዬን ተያያዝኩት፡፡”
ጋዜጠኛው ወ/ሮ ውቢትን የሚሰማት በአግራሞት ነው። “ስራ ፈጣሪ ሰዎች የመክሰር ኃላፊነትን (Risk) ለመውሰድ ደፋሮች ናቸው”፤ የሚለው አባባል ትዝ አለው፡፡ ጋዜጠኛው ሌላ ጥያቄ አነሳ፣
“እና ወ/ሮ ውቢት ትናንትናና ዛሬ እንዴት ናት?”
“ውቢት ትናንትና በትንሽ ቢሮ ውስጥ ተቀጥራ የምትሰራ ነበረች፤ ዛሬ ግን ዘጠኝ ሰራተኞችን ቀጥራ ከተማውን ሁሉ እንጀራ የምትመግብ ናት። ውቢት ትናንትና ወሩን ሙሉ ሰርታ ትንሽ መቶ ብሮችን የምትጠብቅ ነበረች፤ ዛሬ ግን በወር በመቶ ሺ ብሮች የምታንቀሳቅስ ሰራተኛ ሆናለች፡፡ ውቢት ትናንትና ጠዋት ሁለት ሰዓት ወደ ቢሮዋ ገብታ ማታ አስራአንድ ሰዓት ላይ ወደ ቤቷ የምትመለስ ሴት ነበረች፤ ዛሬ ግን ከሌሊት እስከ ሌሊት በትጋት የምትሰራ ባተሌ ሆናለች፡፡ ውቢት ትናንትና ረጅም ኪሎ ሜትሮችን በእግሯ የምትኳትን ሴት ነበረች፤ ዛሬ ግን ከአንድም ሁለት መኪኖች ግቢዋን አጣበውታል፡፡ ውቢት ትናንትና እንደማንኛውም ሰው የምትታይ ነበረች፤ ዛሬ ግን በአርዓያነቷ ብዙ ሴቶችን ለስራ የምታነሳሳ ተምሳሌት ሆናለች። ትናንትና ውቢት ለራሷ የዕለት ጉርስ ብቻ የምትደክም ሴት ነበረች፤ ዛሬ ግን ከራሷ አልፋ ለማህበረሰቡና ለትውልዱ የምታስብ ባለ ራዕይ ሆናለች፡፡ ይሄ ሁሉ ለኔ ደስታን ይሰጠኛል፡፡”
ወ/ሮ ውቢት ወደ ስኬት የመጣችባቸው ዓመታት በጣም ቅርብ ቢሆኑም ዘመኖቿን እንዲህ ውብ በሆኑ ንፅፅሮሽ ማቅረብ መቻሏ ጋዜጠኛውን አስገርሞታል፡፡ ንግግሯ መሳጭና ውስጥንም የሚያነቃቃ ነው፡፡
“ወ/ሮ ውቢት ወደ ፊት ምን ታልማለች? ለሴት እህቶቻችንስ ምን ምክር አላት?” ጋዜጠኛው ሌላ ጥያቄ አስከተለ፡፡
“ውቢት ወደ ፊት ብዙ ነገር ታልማለች፤ ይሄንን ስራችንን  በማስፋት ለህብረተሰቡ ተጨማሪ የስራ እድሎችን መፍጠር እንፈልጋለን። እንዲሁም አሁን እንጀራ ከምናስረክባቸው ሆቴሎችና ካፌዎች በተጨማሪ አዲስ አበባ ላይ ሌላ ቅርንጫፍ በመክፈት ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግም እያሰብኩ ነው፡፡
ለእህቶቻችን የምመክራቸው ብዙ ነገር አለኝ። በመጀመሪያ ውስጣቸውን በደንብ ማዳመጥ አለባቸው፤ በሃሳባቸው የመጣው ነገር በእርግጥም ከውስጣቸው ፈንቅሎ የመጣ ነገር መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለባቸው፡፡ ይሄንን ውስጠት ካዳመጡ በኋላ በዙሪያቸው ያሉትን ሰዎች ወይም የቤተሰብ አባላትን ማስረዳትና ማሳመን አለባቸው። አንድ ሴት በውስጧ ልትሰራው በምታስበው ነገር ላይ ቤተሰቧን ማካተትና የእሷ አጋዦች እንዲሆኑ ማድረግ አለባት፤ ምክንያቱም በስራዋ ላይ የሚያበረታቷትም ሆኑ ብትወድቅ የሚያነሷት እነሱ ናቸው፡፡ ገንዘብ ዋጋ የሚኖረው እነዚህን ሁሉ ቅድመ ሁኔታዎች ካስተካከልክ በኋላ ነው። ከዚህ በኋላ በሙሉ እርግጠኝነት ወደምታልመው ስራ መግባት አለባት፡፡ ሃሳቧን፣ ጊዜዋን፣ጉልበቷንና ገንዘቧን ሁሉ በዚያ ነገር ላይ አተኩራ የምትሰራ ከሆነ በእርግጠኝነት ለውጥ ታመጣለች፡፡
እዚህ ላይ ግን ‘ትኩረት’ ስለሚባለው ነገር ትንሽ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ አንበሳ ሲያድን አስተውለህ ታውቃለህ?” ወ/ሮ ውቢት ጋዜጠኛውን ድንገተኛ ጥያቄ ጠየቀችው፡፡
“በቴሌቪዥን አይቻለሁ፤ ያው በተለመደውና ማንኛውም ሰው በሚያይበት መልኩ ነው እኔም የማየው፡፡” ጋዜጠኛው መለሰ፡፡ ወ/ሮ ውቢት በዚህ ነገር ላይ ምን ዓይነት አዲስ ምልከታ ልታሳየው እንደሆነ ለመስማት ጓጉቷል፡፡
“ብዙ ሰው ከአንበሳ የተሳካ አደን ጀርባ ስላለውና ‘ትኩረት’ ስለሚባለው ነገር ብዙም አያስተውልም። አንበሳ ለአደን ከመሮጡ በፊት የተወሰነ ጊዜ ወስዶ የሜዳ አህዮችን እንቅስቃሴ ያስተውላል፤ ከእነሱም ውስጥ አንዷ ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ሊያድናት የፈለጋትን የሜዳ አህያ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደገና ለብቻው በአትኩሮት ይከታተላል። በስተመጨረሻ የሚንደረደረው ያተኮረባትን የሜዳ አህያ ብቻ ለመያዝ እንጂ በመንገዱ ላይ ያጋጠሙትንና የቀረቡትን የሜዳ አህዮች ለመያዝ አይደለም፤ ይሄንን ማድረግ ለእሱ ትኩረትን መበተንና ጉልበትንም ማባከን ነው፡፡ ሁሉም የሜዳ አህዮች የሚበሉ ቢሆኑም እሱ ግን አንዷ ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ መላ ጉልበቱንና ኃይሉን የሚያውለው ያተኮረባት የሜዳ አህያ ላይ ነው፡፡ ጉልበቱንና ኃይሉን የሚያገኘው ደግሞ ከትኩረቱ ነው፤ እናም ይሳካለታል፡፡
ሰዎች በተለይም ሴቶች ከዚህ የአንበሳ ተፈጥሮ ብዙ መማር አለባቸው፡፡ በመላው ህይወት ውስጥ እጅግ የላቀ ኃይል ያለው ‘ትኩረት’ የምንለው ነገር ነው፡፡ የሰው ልጅ ሀብቱ ትኩረቱ ነው፡፡ አሁን ያለንበት ዓለም በተለያዩ የመረጃዎች ጎርፍ የተጥለቀለቀ ነው። ኢንተርኔቱ፣ሬዲዮው፣ቴሌቪዥኑ፣ጋዜጣው፣መጽሄቱ፣ወሬው..ሁሉበተለያዩ መረጃዎችና ዕውቀቶች የታጨቀ ነው፡፡ ትኩረትህን በእነዚህ ሁሉ መረጃዎች ላይ መበተን የለብህም፡፡ ልትሰራው በምትፈልገው በአንድ ነገር ላይ ብቻ አተኩር፡፡ በጣም አስገራሚው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?”
ወ/ሮ ውቢት በንግግሯ ጭራሽ እየተቀጣጠለች ሄደች። ጋዜጠኛው በተመስጦ ያዳምጣታል፤’በግል የንግድ ስራ ላይ እንዲሰማሩ እገዛ የሚደረግላቸው ሴቶች ከሁሉ አስቀድሞ አሁን ወ/ሮ ውቢት የምትናገረውን ንግግር ዓይነት በስልጠና መልክ ይሰጣቸው ይሆን?’ ብሎ ራሱን ጠየቀ፡፡ ወ/ሮ ውቢት ንግግሯን ቀጠለች፣
“በጣም አስገራሚው ነገር ትኩረት ከፈጠራና ከስራ ጥራት ጋር እንዲሁም ከደስታ፣ ከብልፅግናና ከጤንነት ጋር ሚስጢራዊ ግንኙነት መኖሩ ነው፡፡”
ጋዜጠኛው ተገረመ! ‘ትኩረት’ ስለሚባለው ነገር እምብዛም አስቦበት አያውቅም፡፡ አሁን ከወ/ሮ ውቢት የሚሰማው ሁሉ አዲስ ነገር ሆነበት፡፡ ‘እና እነዚህ ሁሉ ነገሮች ‘ትኩረት’ በሚባለው ነገር የመጣሉ ማለት ነው?’ ጋዜጠኛው ተዓምር ሆነበት፡፡ “እንዴት ወ/ሮ ውቢት?” ጥያቄውን ሰነዘረ፡፡
“እኔ እንጀራ በመጋገር ስራ ላይ ከተሰማራሁ አራት ዓመት እንኳን አልሆነኝም፡፡ ሌሎች በዚሁ ስራ ላይ ረጅም ዓመታት የቆዩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሁሉም ግን ስራቸውን የሚያከናውኑበት መንገድ የተለያየ ነው፡፡ ለስራው ያላቸው ትኩረትና ክብርም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ አንድ የማረጋግጥልህ ነገር ቢኖር ስራቸውን በዝቅተኛ ትኩረት፣ በምሬትና በእፍረት የሚሰሩ ሰዎች ስራው ላይ የቱንም ያህል ጊዜ ቢቆዩ አይሻሻሉም፡፡”
“ምናልባት የአቅም ማነስ ከሆነስ?” ጋዜጠኛው በመሀል ገባ፡፡
“ሁሉን ነገር ከአቅም ማነስ ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም፡፡ ባላቸው አነስተኛ አቅም እኮ ስራውን እየሰሩት ነው፡፡ ያችን አቅማቸውን ግን ትኩረት የሚያሳጧትና ምሬትም የሚያበዙባት ከሆነ እሷንም ያጧታል፡፡ ምሬት ማለት በራሱ የተበተነ ሃሳብና ፍላጎት ማለት ነው፤ ግማሽ ልብ እዚህ፣ግማሽ ልብ እዚያ፡፡ የሃሳብና የፍላጎት መበተን የሚያጋጥምህ ደግሞ በስራው እምነትና ደስታ ከማጣት ነው። ይሄንን ማወቅ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። በስራው እምነት ከሌለህና የተበተነ ፍላጎትም ካለህ የሚደረግልህ የገንዘብ ድጋፍ እንኳን ቢኖር በተበተነው ሃሳብህ ልክ ገንዘብህንም በማይረባ ነገር ነው በትነህ የምትጨርሰው፡፡ እኔ ወደ እንጀራ መጋገር ስራ ስገባ ባለቤቴ ከመ/ቤቱ የተበደረልኝ ብር በጣም ትንሽ ነበር፡፡ እናም የተነሳሁት በጣም በትንሽ ብር ነው፡፡ እዛች አነስተኛ አቅም ላይ ግን መላው ትኩረቴን ጨመርኩበት፤ እያንዳንዷን ሽርፍራፊ ሳንቲምና ጊዜ ስራዬ ላይ ነበር የማውላት። ያለበቂ ምክንያት የማባክናት ጊዜና ሳንቲም ታንገበግበኛለች። ነጋ ጠባ፣ ሁልጊዜ የማስበው እንዴት ደንበኞቼን እንደማስደስት፣ እንዴት ስራው እንደሚያድግ ነበር፡፡ በአንድ ነገር ላይ ስታተኩር ያንን ነገር በትጋት የምትፈፅምበት ከፍተኛ ኃይል ማግኘት ብቻ ሳይሆን ያንን ነገር ከሌሎች ሰዎች በተለየና በላቀ ሁኔታ እንዴት ማከናወን እንዳለብህ ሁሉ አዳዲስ ሃሳቦች ይመጡልሃል፤ ባጭሩ የፈጠራ ሰው ትሆናለህ፤ ስራህም ጥራት ይኖረዋል። በዚህም ይበልጥ ደስተኛና ጤነኛ ትሆናለህ፡፡ ስራው እያደገ ሲሄድም ገቢህም በዚያው መጠን እያደገ ይሄዳል፡፡
እናም ሴቶች የትኩረትን ኃይል ማወቅ አለባቸው። መጀመሪያ በምን ዓይነት ስራ ላይ ቢሰማሩ በቀላሉ ውጤታማ እንደሚሆኑ መለየት አለባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን መላው ሃሳባቸውን በዚያ ነገር ላይ ብቻ ማተኮር አለባቸው፡፡ ሃሳብህ በተበተነ ቁጥር ገንዘብህና ኃይልህም አብሮ ይበተናል፡፡ አንድ ሴት መላው አትኩረቷን በምትሰራው ስራ ላይ ብቻ ስታሳርፍ ያ ስራ ለውጥ ማምጣት ይጀምራል፡፡ ስራዋም በፍጥነት ቀና ቀና ማለት ሲጀምር ታየዋለች፡፡ ወዲያውም የሌሎች ደንበኞችን አትኩሮት ማግኘት ትጀምራለች፤ ስራዋ ሌሎችን ሁሉ ይማርካል፡፡ ወደዚህ ከፍ ከፍ የማለት ደረጃ ላይ የምትደርሰው ግን መጀመሪያ ዝቅ ብላ ስትሰራ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጓደኛዬ እንዳለችው ነው - ገንዘቡ ያለው ከታች ነው!!”
ጋዜጠኛው ወ/ሮ ውቢትን የሚያዳምጣት በከፍተኛ ተመስጦ ነው፡፡ ትኩረት የሚባለውን ነገር እንዴት ከፈጠራና ከስራ ጥራት ጋር እንዲሁም ከደስተኛነት፣ ከብልፅግናና ከጤነኝነት ጋር ያገናኘችበት መንገድ ገርሞታል፡፡
የሆነ የሞቲቬሽን ትምህርት የሚከታተል እንጂ ቃለ መጠይቅ የሚያደርግ አልመሰለውም። ወ/ሮ ውቢት የምትናገረው በንድፈ ሃሳብ ሳይሆን በተግባር ያለፈችበትን የህይወት ተሞክሮ ስለሆነ ምክሮቿ በእርግጠኝነትና በስልጣን የተሞሉ ናቸው፡፡ እንደ ወ/ሮ ውቢት ያሉ የንግድ ስራ ክህሎት ያላቸውን ሴቶች የስኬት ሚስጥር በሚዲያ ማቅረቡ በተለይ የተለያዩ እገዛ የሚፈልጉ ሴቶች ላይ የሚፈጥረውን የመነቃቃት ስሜት ሲያስበው በሚሰራው ስራ ተደሰተ፣ ኩራትም ተሰማው፡፡


Published in ህብረተሰብ
Page 2 of 21