በእናንተ ቤተሰብ ስንት ዓመት ተሮጠ?
 እኔ በሩጫ ውስጥ 14 አመት ቆይቻለሁ፡፡ ባለቤቴ ወርቅነሽ ኪዳኔ ደግሞ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እየሮጠች ነው፤ 20 አመት ሞላት ማለት ነው፡፡
ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት ያነሳሳቹህ ምንድን ነው?
ገንዘብ ወይም ስም ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ የተገኘውን ወደ ስራ ውስጥ አስገብተህ ማንቀሳቀስ አለብህ፡፡ ከመንግስት የምታገኘው አበረታች ድጋፎች እንዲሁም ሌሎች አትሌቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ሲሳተፉ ስትመለከት አንተም በእነሱ መነሻነት ትሳባለህ፡፡
የተሰማራችሁበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምንድነው?
ባለ ዘጠኝ ፎቅ ህንፃ እየገነባን ነው፤ አሁን ወደማለቁ ደርሷል፡፡ 22 አካባቢ ደግሞ አራት የሚከራዩ መኖሪያ ቤቶች አሉኝ፡፡ እንደ ሪል እስቴት ማለት ነው፡፡
ከመንግስት የምታገኙት ድጋፍ ምንድነው?
ትልቁ ነገር ይሄ መንግስት ለሙያችን ዋጋ ይሰጠናል፡ ያ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ያበረታታናል፡፡ ሰው ሲበረታታ ደግሞ የመስራት አቅምን ያገኛል፡፡ ሌላው ደግሞ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ በምንሔድበት ወቅት መንግስት አደራ ይሰጥናል፤ ስንመለስ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ይደረግልናል፡፡ ውጤት ላስመዘገቡት ደግሞ የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶችን ያበረክታል፤ መሬትን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ያ ደግሞ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች እንድንሰራበት ይጠቅመናል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም ብዙ ጊዜ ለኢንቨስትመንት የምንጠቀምባቸውን መሬቶች በጨረታ ሳይሆን በመነሻ ዋጋ እንድናገኝ ይደረጋል፡፡ ይሄም ሌላው ከመንግስት የምናገኘው ትልቅ ማበረታቻ ነው፡፡
አትሌቶች ሩጫ ሳያቆሙ ነው ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡት ሁለቱን በአንዴ ለመምራት አያስቸግርም?
እየሮጥክ ቢዝነስን መምራት በጣም ከባድ ነው፤ የምትፈልገውን ያህል እርካታ አታገኝም፡፡ ነገር ግን እንደ ድሮው የቢሮክራሲ ችግር ብዙ የለም፡፡ እየተሻሻለ ነው፡፡ ይሄ ነገሮችን ያቀልልሃል፡፡ በምትፈልገው ቢዝነስ ውስጥ ገብተህ ልትሰራ ትችላልህ፡፡ ትልቁ ችግር ግን አንተ የምትፈልገውን አይነት የስራ ጥራት መሬት ላይ አርፎ አታገኝም፡፡ በወረቀት ላይ የምትያቸው ጥሩ ሃሳቦች በተግባር ሲከናወኑ አታይም፡፡ ይሄ ትልቅ ችግር ነው፡፡
አብዛኞቻችሁ በህንፃ ግንባታ ላይ ያተኮራችሁበት ምክንያት ምንድነው?
ግንባታ ቋሚ ንብረት ነው፤ የምታየውን ነገር ነው የምታስቀምጠው፡፡ ለምሳሌ ኢንዱስትሪ ውስጥ ወይም ማምረት ውስጥ ብትገባ ውጤታቸው ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው የሚታየው፡፡ በተጨማሪም ቀን በቀን ሳይንሳዊ ክትትልን ይፈልጋሉ፡፡ ያን ለማድረግ ደግሞ ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ ህንፃ ላይ ኢንቨስት ስታደርግ ከሌላ ሙያ ጋር ለምሳሌ ከአትሌቲክስ ጋር ልታስኬደው ትችላለህ፡፡ የፋብሪካ ስራ ግን ሙሉ ጊዜና ትኩረትህን ስለሚፈልግ ይከብዳል፡፡
በቅርቡ የጀመርከው የተራራ ላይ ሩጫ እንደ ኢንቨስትመንት ይቆጠራል?
ለጊዜው እንደ ኢንቨስትመንት አይቆጠርም፡፡ እንደውም ይህንን ሩጫ በማድረጋችን ከ500ሺ ብር በላይ ከስረናል፡፡ ዋናው ነገር ግን እሱ አይደለም፡፡ የኛ ጥረት በትንሹም ሊሆን የሀገራችንን ገጽታ መገንባት ነው፡፡ ስለ ተራራው ሩጫ በ“ሱፐር ስፖርት” የ45 ደቂቃ ሽፋን ለ3 ቀናት ተሰጥቶት ተዘግቧል፡፡ በስፔን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ሽፋን አግኝቷል፡፡ የተለያዩ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎችም ሽፋን ሰጥተውታል፡፡ ከዚያ በኋላ “እውነት ይሄ ኢትዮጵያ ነው ወይ?” የሚሉ ጥያቄዎች ሁሉ መጥተዋል፡፡ ይሄ ለኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ነገ ኢንቨስትመንት ሊሆን ይችላል የሚል እምነት ግን አለን፡፡
ቢዝነስ ማስተዳደር ምን ይመስላል?
ባለቤቴ ከኔ በላይ ብዙ የሰራችና የተከበረች ናት፡፡ ለዚህ አንፃር በሩጫውም ሆነ በስራው ላይ ትደግፈኛለች፡፡ ሁለታችንም አንድ አይነት ሙያ ነው ያለን፡፡ ሁለታችንም የአትሌቲክስ ቋንቋ ነው የምናወራው፡፡ ስለዚህ በቀላሉ ለማከናወን ይረዳናል፡፡
ሌሎች ያሰባችሁቸው የኢንቨስትመንት ዕቅዶች አሉ?
ኢንቨስትመንት መሰረት ነው፤ አንዴ መሰረቱ ከተጣለ፣ ከዚያ በኋላ ያለው የማገለባበጥ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በባንክ በኩል ያለውም ነገር የተመቸ ነው፤ የተሻለ ነገር ሰርተህ የምታሳይ ከሆነ አብረውህ ይሰራሉ፡፡ ቢዝነስ ብቻውን የሚጓዝ ነገር አይደለም፡፡ ቢዝነስ አብሮ መስራት ነው፡፡ ከህብረተሰቡ ጋር ተደማምጠህ ስትሰራ ውጤታማ ትሆናለህ፡፡
እስካሁን ምን ያህል ገንዘብ ኢንቨስት አድርገችኋል?
ተደምሮ የተቀመጠ ይህ ነው የሚባል የገንዘብ መጠን የለም፡፡ ስራው ሲያልቅ የሚሰላ ይሆናል፡፡ ቀላል ገንዘብ ግን አይመስለኝም፡፡ ከ50-60 ሚሊዮን ብር ይጠጋል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛ ከህዝብ የወጣን ሰዎች ነን፤ ስለዚህ ህዝቡን ማገልገል አለብን፡፡ እንደምናገለግል ህዝቡ ሊያውቅ ይችላል፤ ሳናገለግልም ቀርተን ይሆናል፡፡ ይህንን ለህብረተሰቡ በማሳወቅ ረገድ ሚዲያ ትልቅ ሚና አለው፡፡ እኔን ጨምሮ ሌሎች አትሌቶች የሚሰሩትን ስራ በምንሰራው ስራ ክብር ለሰጠን ህዝብ ክብር እየሰጠን መሆኑን ለማሳየት ሚዲያ ወሳኝ ነው፡፡

ባለፈው ሰሞን በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለአራት ቀናት የተካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አገሪቱ ወደፊት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮችን ለማዘጋጀት የምትችልበትን አቅምና ብቃት ማሳየቱ ተገለፀ፡፡ በሻምፒዮናው አስተናጋጇ ኢትዮጵያ በውድድር መስተንግዶ ብቃት ከመደነቋም በላይ፤ በአዲስ አበባ የነበረው የስፖርት አፍቃሪ ለሻምፒዮናው በሰጠው ማራኪ ድባብ ከተለያዩ አካላት ምስጋና ቀርቧል፡፡ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን በሰጠው መግለጫ ሻምፒዮና ስኬታማ እንደነበር አስታውቆ በሻምፒዮናው ታሪክም ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የተመልካች ቁጥር ያስተናገደች አገር እንደሆነች አመልክቷል፡፡
ሻምፒዮናው የምንግዜም ምርጥ ለምን ተባለ
ሻምፒዮናው በተመልካች ብዛት፤ በዝግጅት እና በመስተንግዶ፤ በደማቅ ፉክክር እና በቴሌቭዥን ስርጭት በታሪክ የምንግዜም ምርጥ እንደነበር የተናገሩት የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ማሀመድ ካልካባ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናውን ያለአንዳች ችግር በማስተናገዷ ወደፊት ሌሎች ውድድሮችን የምታስተናግድበትን እድል እንደሚያሰፋውም ገልፀዋል፡፡በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትና በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የውድድር ዝግጅትና የቴክኒክ ኮሚቴዎችን የመሩት ሞሪሲሽያዊ እና የኬንያ አትሌቲክስ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዴቪድ ኦኮዩም የኢትዮጵያ ዝግጅትና መስተንግዶ እንዳስደነቃቸው ተናግረው ከመስተንግዶ ባሻገር በማራኪ ድጋፍ እና የተሳትፎ ውጤት የታጀበ መስተንግዶ መታደማቸው አርክቶናል ብለዋል፡፡ ሁለቱ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን አመራሮች ከደቡብ አፍሪካ ከኬንያና ከምራብ ባሻገር ወደፊት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ መደረግ ያለባቸውን ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች እንደ ዓለም ሻምፒዮና እና ኦሎምፒክ ለማስተናገድ ኢትዮጵያም እጩ የምትሆንበት አቅም እንዳላት መስክረዋል፡፡
የአትሌቶች ማናጀር የሆነውና በግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽን ስር የበርካታ ታላላቅ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዲያሬክተር እና በሻምፒዮናው የውድድር ዲያሬክተር የነበሩት አቶ ዱቤ ጅሎ ደግሞ ኢትዮጵያ ከ6 ዓመት በፊት ካስተናገደችው 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተሻለ 12ኛውን የአፍሪካ የወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በተሟላ ብቃትና ስኬት ማስተናገዷን ገልፀዋል፡፡ የወጣቶች ሻምፒዮናውን ስኬታማ ለማድረግ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ከመንግስትና ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት ተቋማት በቅንጅት መስራቱን የጠቀሱት አቶ ዱቤ ጅሎ ፤ ወደፊት መሠል የአፍሪካ አትሌቲክስ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯልና ይላሉ፡፡  በወጣቶች ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በነበራት ተሳትፎ በተለይ በሜዳ ላይ የስፖርት ውድድሮችና በአጭር ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ጠንካራ እና በሜዳልያ ውጤት የታጀበ ተሳትፎ ማድረጓ በአገሪቱ በማካሄዱ አካዳሚዎች፣ የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች መልካም ተግባራት መከናወናቸውን እንደሚያመለክትም አቶ ዱቤ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ኤጀንት ሆኖ የሚሠራው ጌታሁን ተሰማ በበኩሉ፤  የወጣቶች ሻምፒዮናው በአዲስ አበባ በድምቀት መካሄዱን አድንቆ፣ የወደፊት የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮኖች የሚወጡበት መድረክ በመሆኑ የተሳትፎ አቅም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ምክር ሰጥቷል፡  የናይጀሪያ የወጣቶች የአትሌቲክስ ቡድን የአጭር ርቀት ሯጮች አሰልጣኝ ኩስሊ ሞናልዬ በሰጡት አስተያየት ናይጀሪያ ወጣትና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት በስፋት እንደምትሠራ ጠቅሰው፣ በመላው አገሪቱ በመንግስት ስር ያሉ አካዳሚዎችና በግል የሚከፈቱ ማሰልጠኛዎች ውጤታማ እንዳደረጋቸው አስገንዝበዋል፡፡ በናይጀሪያ አትሌቲክስ ለወጣቶች ላይ ትኩረት በመስጠት ይሠራል ያሉት አሰልጣኙ በአካዳሚዎች አሠራር ሁለት ደረጃዎችን እንደሚከተሉ ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ዕድሜያቸው ከ13-15 የሚሆኑ ታዳጊዎች ከ2-4 ዓመት የሚሠለጥኑበት ሲሆን ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ16-19 የሚሆናቸው ወጣቶች ለ2ና 3 ዓመታት ሠርተው ለፕሮፌሽናል ደረጃ የሚደርሱበት ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው አሰልጣኝ በበኩላቸው ወጣት አትሌቶችን ለማሠራት የአገራቸው የከፍተኛ የስፖርት ብቃት ማሰልጠኛ ተቋማት በመላው የአገሪቱ ክልሎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ በእነዚሁ አካዳሚዎች ከ3ሺ በላይ ወጣቶች በሁሉም የአትሌቲክስ የሜዳና የትራክ ስፖርቶች ከፍተኛ ስልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡  በደቡብ አፍሪካ በት/ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚደረጉ ዓመታዊ ውድድሮችንም ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ምቹ መድረኮች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
የሜዳልያው ሰንጠረዥና የኢትዮጵያ ማራኪ ተሳትፎ
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ብዛት ቀዳሚ ሆና ብታጠናቅቅም በከፍተኛ የወርቅ ሜዳልያ ብዛት አንደኛ ደረጃ ለማግኘት የቻለችው ናይጄሪያ በ12 ወርቅ፣ በ8 ብርና በ7 ነሐስ ሜዳልያዎች ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ9 ወርቅ፣ በ7 ብርና በ7 የነሐሰ ሜዳሊያ ሁለተኛ ስትሆን ኢትዮጵያ በ6 ወርቅ፣ በ12 ብርና በ10 የነሐስ ሜዳሊያ ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች፡፡ናይጄርያ  የሜዳልያ ሰንጠረዡን በአንደኛነት በመምራት ለሁለተኛ ተከታታይ ሻምፒዮና ክብሯን አስጠብቃለች፡ ሁለቱ አትሌቶች የአጭር ርቀት ሯጩ ዲቫይን ኦዱዱሩ በወንዶች እንዲሁም በዝላይ ውድድሮች እና በ100 ሜትር ሩጯ ኤሴ ብሩሜ በሴቶች ሶስት የወርቅ ሜዳልያዎችን በማግኘት ስኬታማ ነበሩ፡፡ የናይጄርያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በሻምፒዮናው በተገኘ መነቃቃት ወደፊት በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች አትሌቶችን ለማፍራት ለስፖንሰሮች ድጋፍ ጥሪ እንዳቀረበ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ፍፁም የበላይነት ካደረጉባቸው የመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ውድድሮች በተጨማሪ በሜዳ ላይ ስፖርቶች እና በአጭር ርቀት ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ችለዋል፡፡ በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተካፈሉት 39 አገራት 550 ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ  በሻምፒዮናው ከቀረቡት 127 ሜዳልያዎች  (43 የወርቅ 43 የብርና 41 የነሐስ)   19 አገራት የየድርሻቸውን አግኝተዋል፡፡በወንዶች ምድብ 209 በሴቶች ምድብ 145 አትሌቶች የተካፈሉ ሲሆን በሻምፒዮናው ዳኝነት፤ አመራር እና ማስተናበር ከ172 በላይ የስፖርት ባለሙያዎች ነበሩ፡፡
ግብፅ በ13 ሜዳልያዎች (5 ወርቅ 3፣ ብርና 5 ነሐስ) ፤ ኬንያ በ12 ሜዳልያዎች (4 ወርቅ ፣  5 ብርና 3 ነሐስ) ፤ አልጄርያ በ5 ሜዳልያዎች (2 ወርቅ ፣ 1 ብርና 2 ነሐስ)  ፤ ቦትስዋና በ3 ሜዳልያዎች  (2 ወርቅና 1 ብር)  ፤ ሞሮኮ በ5 ሜዳልያዎች (1 ወርቅ ፣ 1 ብርና 3 ነሐስ)  ፤ ኡጋንዳ በ3 ሜዳልያዎች (1 ወርቅና 2 ነሐስ)  ፤ ቱኒዚያ በ2 ሜዳልያዎች (1ወርቅና 1 ነሐስ)  ፤ ዚምባቡዌ፣ ኮትዲቯርና እና ናሚቢያ እያንዳንዳቸው 1 የብር ሜዳልያ እንዲሁም ዛምቢያ፣ ኮንጎና ማዳጋስካር እያንዳንዳቸው 1 የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት ከ4 እስከ 14 ያለውን ደረጃ አከታትለው አግኝተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ካሰለፈቻቸው አትሌቶች መካከል 2 አትሌቶች ከሜዳልያና ከዲፕሎማ ውጪ ሲሆኑ 2 አትሌቶች ከውድድር ውጪ መሆናቸውን ያስታወቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ፌደሬሽን 76 አትሌቶች ከወርቅ /ከ1ኛ/ እስከ ዲፕሎማ /7ኛ/ ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን እንዳጠናቀቁ በማመልከት ሁኔታውይህ የተተኪዎችን የነገ ተስፋ አመላካች ውጤት በማለት አድንቆታል፡፡
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ 28 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የበላይ ነበረች፡፡ ከሰበሰበቻቸው 6 የወርቅ ሜዳሊያዎች 5ቱ በሴቶች የተገኙ ናቸው፡፡ ዮሚፍ ቀጀልቻ በወንዶች 5 ሺህ ሜትር ለሀገሩ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ ሲወስድ፤ ሌሎቹ 5 የወርቅ ሜዳልያዎች በዘውዴ ማሞ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሴቶች፤ በእታገኝ ማሞ 5ሺህ ሜትር ሴቶች፤ በኋላየ በለጠ 5ሺህ ሴቶች የዕርምጃ ውድድር ፤ በንጉሴ ብረስ በ3ሺህ ሜትር ሴቶች እንዲሁም በዳዊት ስዩም 1ሺህ 5 መቶ ሜትር ሴቶች አማካኝነት የተገኙ ናቸው፡፡
አስደናቂው የቲቪ ቀጥታ ስርጭት እና ቲቪ ሚዲያ ስፖርት
ለሻምፒዮናው የ4 ቀናት ውድድሮች በ22 የአፍሪካ አገራት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን በመስጠት ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር የሰራው ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ያደረገው ቲቪ ሚዲያ ስፖርት ነበር፡፡ በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች አዘጋጅነት፤ የስርጭት ሽፋን፤ የማርኬቲንግ እና የመረጃ ስራዎችን በመስራት በአጭር ጊዜ ስኬታማ የሆነው የብሮድካስት ኩባንያው፤ ከበርካታ አገራት የስፖርት ፌደሬሽኖች ጋር በመስራት በተለይ ለአፍሪካ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ እየተሳካለት መጥቷል፡፡
በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 14 ካሜራዎች ለውድድሩ የቀጥታ ስርጭት ተግባር ላይ የነበሩ ሲሆን ከቲቪ ሚዲያ ስፖርት 45 ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከ100 በላይ ባለሙያዎች በቅንጅት ሰርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሻምፒዮናው የቀጥታ ስርጭት ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን የሚገልፁት የቲቪ ሚዲያ ስፖርት መስራች ሄይዲ ሃመል፤ ኮርፖሬሽኑ ያሉት ካሜራዎች እና የድምፅ መሳርያዎች ከፍተኛ ደረጃ እና ብቃት ያላቸው መሆኑ እንዳስደነቃቸው ለስፖርት አድማስ ተናግረዋል፡፡ የፎቶ ፊኒሽ፤ የመረጃ እና የሰዓት አያያዝን ለማከናወን ተግባር ላይ የዋሉ መሳርያዎች የወቅቱን ቴክኖሎጂ በብቃት ያሳዩ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡ የውድድሩ ስርጭት በአፍሪካ ብቻ አለመወሰኑን  የገለፁት ሄይዲ ሃመል፤  በአፍሪካ የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሳተላይት በመጠቀም በአንዳንድ አውሮፓ አገራት ሽፋን ለመስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡
በሞስኮ የተካሄደውን 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በዚያው በራሽያ የተደረገውን የሶቺ የክረምት ኦሎምፒክ እንዲሁም በሞሮኮ የተደረገውን የዓለም ክለቦች ዋንጫን ያስተላለፈው ቲቪ ሚዲያ ስፖርት በስፖርቱ ዙርያ ሲሰራ ከ11 ዓመት በላይ ሲሆነው በአውሮፓ እግር ኳስ፤ በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ የስራ ድርሻ ያለው ሲሆን በተለይ በአፍሪካ የስፖርት እንቅስቃሴ የቲቪ ስርጭትን ለማሳደግ በከፍተኛ ዓላማ በመያዝ እንደሚንቀሳቀስ ይገልፃል፡፡ ቲቪ ሚዲያ ስፖርት በ2016 በብራዚል ሪዮዲጄነሮ የሚደረገውን 21ኛው ኦሎምፒያድ፤ ከ2014 ጀምሮ እስከ 2017 ሁሉንም የአይኤኤፍ ውድድሮች፤ ከ2004 ጀምሮ የአውሮፓዎቹን ታላላቅ ሊጎች የጣሊያኑን ሴሪኤ እና የጀርመኑን ቦንደስ ሊጋ በ43 አገራት በቲቪ የማሰራጨት ሙሉ መብቱን ይዟል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ብዙ ጋሻ ቡና መሬት፣ ይጭኑት አጋሠሥ ይለጉሙት ፈረስ ያላቸው የበለፀጉ አባት ያሉት ልጅ አባቱን እንዲህ ይላቸዋል፡፡
“አባዬ”
“ወይ”
“እንግዲህ ለአቅመ - አዳም ደርሻለሁ፡፡ እንዴት አድርገህ ነው የምትድረኝ?” ሲል ይጠይቃል፡፡
አባቱም፤
“ለመሆኑ ኃላፊነት ለመቀበል ዝግጁ ነህ ወይ?”
“አዎን፤ ዝግጁ ነኝ”
“እንግዲህ ለሁሉም ወሳኙ የቡና አዝመራችን ነው”
“እንዴት አባዬ?”
“አየህ ከአሁኗ ሰዓት ጀምረህ መሬቱን መኰትኮት አለብህ፡፡ አረሙን መንቀል አለብህ፡፡ ውሃ ማጠጣት አለብህ፡፡ ከዚያ በትዕግስት እስከአዝመራው ሰዓት መጠበቅ አለብህ”
“ከዚያስ አባዬ?”
“ከዚያ ደግሞ ትለቅማለህ?”
“ቡና ለቃሚ ሠራተኞች አሉን አይደለም እንዴ?”
“አሉን”
“ታዲያ እኔ ለምን እለቅማለሁ?”
“አየህ ኃላፊነት የበላይ ተቆጣጣሪነትን ብቻ አይደለም የሚጠይቀው፡፡ ወርደህ ሥራውን ማወቅ፣ አውቀህም ሠርተህ ማየትን ይጠይቃል፡፡”
“ከዚያስ በኋላ?”
“ከዚያማ አዝመራው የሰጠና ያልሰጠ መሆኑ ተጣርቶ ያንተም የእኔም ዕጣ - ፈንታ ይወሰናል”
“ይሄ ምን ማለት ነው አባዬ?”
“ይሄ ማለት አዝመራው የሰጠ ከሆነ አንተን ድል ያለ ድግስ ደግሼ እድርሃለሁ፡፡ የማር - ጨረቃህንም (Honey - moon) ወይም የጫጉላ - ሽርሽርህንም በየባህሩ ዳርቻ አደርግልሃለሁ፡፡
በአንፃሩ አዝመራው የሰጠ ካልሆነ ግን አንተም አታገባም፡፡ እኔም ያለችኝን ሚስት እፈታ ይሆናል!” አሉት፡፡
***
አዝመራው መስጠት አለመስጠቱ የእኛ መሠረታዊ ጥረት ውጤት ነው፡፡ ያልዘራነውን፣ ያላረምነውን፣ ያልኮተኮትነውን ማጨድ፣ ማዝመር አንችልም፡፡ ለምርጫ መዘጋጀት ማለት ነው፡፡ “ከሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ሩጫ መውጣት አለብን፡፡ በአንፃሩ ‘ገባው አልገባው አይደለም የፖለቲካ ምሥጢሩ፤ ተቀበለ አልተቀበለ ነው’ ከሚለውም የባለ ድሎች መዝሙር  መላቀቅ አለብን፡፡ ዲሞክራሲ ሂደት ነውና አሸናፊ ተሸናፊ የሚሆንበት ጊዜ እንደሚኖር አንርሳ፡፡
“ተቃዋሚዎች አንዴ በርቶ ተቃጥሎ ከመቅረት (Burn bright and burn out) የተሻለ መላ ማሰብ አለባቸው፡፡ ሁሉን አቀፍ ራዕይ ያለው ሥርዓት መፍጠርን ማሰብ አለባቸው፡፡ ሥርዓቱ ቢወድቅ የሚኖረን ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ምን መሆን አለበት? እስከሚል ድረስ ማሰብ ያሻቸዋል” ትለናለች ኖኦሚ ክላየን፡፡
አንድ መምህር ተማሪዎቹን ሲያስተምር፤
“አንዳንዴ ትናንሽ የነገ እርምጃዎችን የግድ መቀበል ይኖርብናል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‘እንደ ጐሽ መሮጥ ይኖርብናል’ ያለውንም አንርሳ” ይላል፡፡ ሁልጊዜ ሩጫ አይመረን ማለቱ ነው፡፡  
ሎሬት ፀጋዬ እንደሚለን፤ “በሁሉም ጐራ ላሉ የአፍሪካ የሕዝብ መሪዎች፣ ገዢዎችና በስሙ ለሚነሱ አማጺያን ያለኝ መልዕክት አንድ ብቻ ነው፡፡ መርኋችሁ እውነት ለዲሞክራሲ ከሆነ ‘እኔ አውቅልሃለሁን’ ትታችሁ ሕዝቡን ተከተሉ” የሚል ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ ይሄዳል፣ ይንቀሳቀሳል፤ ግመሉንም እየነዳ ይሄዳል፡፡ ግን አንድ ቦታ ሲደርስ “አትሒድ ከእንግዲህ በኋላ ያንተ አገር አይደለም” መባል የለበትም፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ተልዕኮ መሆን ያለበት የህዝቡን የኑሮ ጉዞ፣ ነፃነቱን፣ ክብሩን፣ መብቱን፣ ማመቻቸትና መጠበቅ ነው መሆን የለበት፤ እንጂ የራሳቸውን ወይም የአዛዦቻቸውን ፍላጐት ማሟላት አይደለም፡፡ አዛዥ ሕዝብ ነው መሆን ያለበት!” ይህን ሁሉም እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ማወቅ ነው የሚገባው፡፡
“ያለመስዋዕትነት ድል የለም” የሚለው የዱሮ መፈክር ዛሬም ደርዝ አለው፡፡ እጅግ ረዥም መንገድ እንሄዳለን ብሎ ለተነሳ ፓርቲ ወይም ድርጅት፤ “ጉዟችን ረዥም ትግላችን መራራ” የሚለው ከዓመታት በፊት የነበረ መፈክር ይዘቱ ለዛሬም ፋይዳ አለው ብሎ ማሰብ የአባት ነወ፡፡ በተተነኮስን ቁጥር አገር ይያዝልን ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ መተንኮስና መገፋት ብቻ አይደለም መስዋዕትነት፡፡
ጨርሶ ከጨዋታው መባረርስ ቢሆን ብሎ ማሰብ ያሻል፡፡ አንድ ልብ፣ አንድ አፍ፣ አንድ ማህበር ሆነው እንዲኖሩ ማሰብ ቀዳሚ ነገር ነው!
“ከደደብ ሰዎች ጋር አትከራከር፡፡ ወደነሱ ደረጃ ዝቅ ያደርጉሃል፡፡ ከዚያ በኋላ በልምዳቸው ያሸንፉሃል!” (ማርክ ትዌይን)
ተፎካካሪያችንን በቅጡ ማወቅ፣ ድልን ያለጉራ፣ ሽንፈትን በፀጋ ለመቀበል ይጠቅማል፡፡ ዞሮ ዞሮ ባለጉዳዩ ብቻ የሚያቀው ነገር ሁሌም አለ፡፡ “የመቃብር ሥቃይ የሚታወቀው ለሟቹ ብቻ ነው” (The torture of the grave is known only to the dead) የሚለው የስዋሂሊ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ካለፈው የቀጠለ
ባለፈው እትም የጽሑፌ ክፍል፣ ዴሞክራሲ እና ነጻነት ለመጎናጸፍ ይበጃሉ የሚባሉት ተቋማትን ገዥው ግንባር ኢሕአዴግ እንደምን መንፈሳቸውን ቀይሮ የራሱ የፖለቲካ መገልገያ እንዳደረጋቸው፤ የምርጫ ሥርዐቱን በምሳሌነት በማንሣት ለማብራራት ሞክሬአለኹ፡፡ እንደ ፓርላማ፣ የፍትሕና የሚዲያ፣ የመድበለ ፓርቲና የምርጫ ሥርዐት ማስፈጸሚያ ተቋማት በአገዛዙ የታለመላቸውን ዓላማ ለማሳካት አወቃቀራቸው ብቻ ሳይኾን ኦሆ ባይ አንቀሳቃሾቻቸውም/yes men/ ያስፈልጓቸዋል። ያለ ኦሆ ባይ አንቀሳቃሾች መዋቅሮቹ እንደማይሠሩ ብረዳም በምሳሌነት በአነሣኹት የነጻ እና ፍትሓዊ ምርጫ አወዳዳሪ ተቋም አግባብ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እና ለሰብሳቢው ፕሮፌሰር መርጋ በቃና የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለማቅረብ እወዳለኹ፡፡
በ‹‹አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ›› አመራር መካከል ተፈጠረ ለተባለው ውዝግብ፣ የሚመሩት ተቋም በተለይም እርስዎ ጉዳዩን ተቀብለው በዐደባባይ ለማሸማገል መሞከርዎ አስገርሞኛል፡፡ ምርጫን ለማስተዳደር የተመሠረተ ተቋም ጉዳዩን በዐደባባይ በቴሌቪዥን ሽምግልና ለመፍታት መሞከሩ በየትኛው ሕጋዊ፣ ሞራላዊና ልማዳዊ አሠራር ነው ተቀባይነት የሚኖረው?
እርስዎ በ‹‹ታዛዥነቱ›› የፈረዱለትን የፓርቲውን አንድ ቡድን የሚመራው አቶ ትዕግሥቱ አወሉ፣ በፓርቲው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት በአባሉ ዘንድ የነበረው የተቀባይነት ኹኔታ ለራሱ ከሰጠው ድምፅ በቀር በድምፅ አልባነት የተገለጸ ነበር፡፡ ይህን ከራሱ ውጭ አንዳችም የድጋፍ ካርድ ያላገኘበትን መድረክ እና ብያኔውን ችላ ብሎ ሌላ ስብስብ ፈጥሮ በአቋቋመው መድረክ አካሔድኹት ያለውን የምርጫ ውጤት ቦርዱ እንደምን ተቀበለው?
በአቶ አበባው መሐሪ የሚመራው የመኢአድ ቡድንና የኢንጅነር ግዛቸው ሺፈራው ‹‹የአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትሕ ፓርቲ›› ሊዋሐዱ ቅድመ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ጽ/ቤትዎ፣ ‹‹የአቶ አበባው መኢአድ ያላሟላው ጉዳይ አለ፤›› በሚል ምክንያት አመራሩ ሕጋዊ እንዳልኾነና መዋሐዱም ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጸው ነበር፡፡ ይህን ታላቅ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ኃይል መዋሐድ አክሽፈው ሲያበቁ፣ በመኢአድ አመራሮች መካከል ልዩነት ሲፈጠር ደግሞ ትላንት ሕጋዊ አይደለም ያሉትን የአቶ አበባው መሐሪ አመራር ዕውቅና የመስጠትዎ የፖሊቲካ ዥዋዥዌ በእጅጉ አስገርሞኛል፤ አሳዝኖኛልም፡፡    
፫. ዐውደ ፍትሕ
በዚኽ ሦስተኛው የመጣጥፉ ክፍል በጣም አሳሳቢ በኾነው የፍትሕ ጉዳይ ላይ አንዳንድ ሐሳቦችን አቀርባለኹ። ፍትሕን በሚመለከት፣ በአገራችን ካለፈው ሥርዐት በተለየ የተወሰኑ መሻሻሎችና መስተካከሎች ቢታዩም፣ አኹንም ቢኾን ትልቅ የፍትሕ ክፍተት አለ የሚል እምነት አለኝ።
በፍትሕ ኀልዮት ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ድርሳናት የጻፉ ሰዎች እንደሚያቀርቡት፣ ‘ፍትሕ’ በጥቅሉ ኹለት ዐበይት መደቦችን የያዘ ፅንሰ ሐሳብ ነው፤ እኒኽም ‘ሰብስታንቲቭ ጀስቲስ’ (ፍሬ-ነገራዊ ፍትሕ) እና ‘ፕሮሲጀራል ጀስቲስ’ (ወጋዊ ፍትሕ) ይባላሉ። ከኹለቱ የፍትሕ አመለካከቶች በመነሣት በአገራችን ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች ለማሳየት እሞክራለሁ።
ስለ ‘ሰብስታንቲቭ ጀስቲስ’ በምናወራበት ጊዜ፣ በርእሰ ነገሩ ላይ ወሳኝ ድርሳን የጻፉትንና ለብዙ ዓመታት በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩትን ጆን ሮውልስን ሳንጠቀስ አናልፍም። ‘የፍትሕ ንድፈ ሐሳብ’ (A Theory of Justice) በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ጆን ሮውልስ ፍትሕን በተመለከተ ባስቀመጡት አስተምህሮ፣ አንድን ሥርዐት ፍትሐዊ ነው የምንለው÷ ዜጎች በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ኹሉም ተቋማት ውስጥ ገብተው ሥራ ለመያዝ ወይም ለመገልገል (በጨረታም ኾነ በሌላ መልኩ ለመሳተፍ) በፆታ፣ በብሔር እና በመደብ ሳይኾን እንደየችሎታቸው ብቻ ተመርጠው ለመሳተፍ ሲችሉ ነው። የአገራችን ብሂል “ከዕንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከሰው መርጦ ለሹመት” ይለዋል፤ የጆን ሮውልስን ሐሳብ። በአኹኑ ሥርዐት ግን ያ ተቀልብሶ “ከዕንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከብሔር መርጦ ለሹመት” ኾኗል።
በኹለተኛ ደረጃ፣ ፍትሕን በሚመለከት ማይክል ቫልዘር የተባለው ዕውቅ አሜሪካዊ ምሁር ‘Spheres of Justice’ በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ያሰፈረውን እንመልከት። ቫልዘር ያቀረበው ሐሳብ ጥንት አፍላጦን ስለ ‘ፍትሐዊት ከተማ’ ካቀረበው የፍትሐዊነት ሐሳብ ጋር ትስስር አለው። አፍላጦን የሰው ልጅን በሦስት መደቦች ይከፍላል፤ አንደኛ፣ ኅሊናዊነት ያመዘነባቸው፤ ኹለተኛ፣ ልባምነት ያመዘነባቸው፤ እና ሦስተኛ፣ አምሮታዊነት ያመዘነባቸው ናቸው። አፍላጦን፣ እኒኽን መደቦች ከለየ በኋላ፣ አንዲት አገር ፍትሐዊነትዋ የሚሠምረው ሦስቱ መደቦች በአገሪቱ ውስጥ ልከኛ ቦታዎቻቸውን ሲይዙ መኾኑን ይናገራል፡፡ ይኸውም ኅሊናውያኑ ሀገር መሪ፣ ልባውያኑ ሀገር ጠባቂ፣ እና አምሮታውያኑ አምራች ሲኾኑ ነው፣ ይላል።
ቫልዘርም በበኩሉ፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ፍትሕ የሚዋቀርባቸው ልዩ ልዩ ዐውዶች አሉ፤ የእኒኽም ሥምረትና ኅብር ለማኅበረሰቡ የፍትሕን መልካም ጽዋ ያስጎነጫሉ፤ ነገር ግን ከዐውዶቹ መካከል አንዱ እንኳ ያለቦታውና ያለግብሩ ከዋለ ፍትሕ ትዛባለች። ለምሳሌ፣ ገንዘብ አንድ የራሱ ተገቢ ዐውድ ማለትም የሚንቀሳቀስበት የራሱ ተገቢ ምሕዋር አለው፡፡ ከዚኽ ዐውድ ወጥቶ ወደ ሌላ ዐውድ ውስጥ ጥልቅ ቢል ግን፣ ያኔ ፍትሕ አጉል ትኾናለች። ገንዘብ ከመገበያያነት ዐውድ ወጥቶ ለፖለቲካዊ ተጽዕኖ ማሳረፊያነት ከዋለ፣ ኀጢአት ማስተስረያ ከኾነ፣ የዳኝነት ውሳኔን ካስለወጠ… ወዘተ የአንዲት አገር የፍትሐዊነት ዐውዶች መስመሮቻቸው ይዘበራረቃሉ።
ዛሬ በአገራችን ‘ብሔር’ እና ‘ልማት’ ዐውዳቸውን ስተው ያለግብራቸው ውለዋል። በመጀመሪያ ‘ብሔር’ የሚለውን ብንወስድ፣ የብሔር እኩልነትና ተዋፅኦ በሚል ፈሊጥ፣ የግለሰቦችን የብሔር አባልነት ብቻ በማየት ዐቅማቸው ከሚፈቅደው በላይ ሓላፊነት እንዲሸከሙ ኾነዋል። ይህ ደግሞ በሹመትና በሥራ ውጤት መሀል ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል። እዚህ ላይ፣ የብሔር እኩልነት የሚለው ጥሪ በጎ ቢኾንም፣ አኹን ግን ከገደቡ ወጥቶ፣ ጥንት ሰዎች ሹመትን በሐረገ ትውልድ/ውልደት/ መስፈርት ከሚያገኙበት ባላባታዊው ሥርዐት ጋራ ተመሳስሏል።
ከአንዲት አገር የፍትሕ ዐውዶች መካከል አንዱ ፖለቲካ ነው፤ ፍትሐዊ ይኾንም ዘንድ በውስጡ ሌሎች ዐውዶች ሊጥሱት አይገባም። በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ግን የፖለቲካ ምሕዋሩ በሌሎች ዐውዶች እየተጣሰ ነው። ብሔር ያለቦታው፣ ያለግብሩ ለፖለቲካዊ ሹመት በመስፈርትነት ውሏል፤ በዚኽም የፖለቲካ ዐውድ ተጥሷል፤ ይህም በጥቅሉ የአገሪቱ ‘ዐውደ ፍትሕ’ ላይ ተጽዕኖውን አሳርፏል። ለፖለቲካዊ ሹመት መስፈርቱ ፖለቲካዊ አስተዳደርን መቻል እንጂ፣ የዚኽኛው ወይም የዚያኛው ብሔር አባል መኾን የለበትም።
በሌላም በኩል እንዲኹ፣ ኢሕአዴግ በተደጋጋሚ “አመርቂ ግስጋሤ እያስመዘገብኹ ነው” የሚልበት የልማት ዐውድ የራሱን ምሕዋር ጥሶ ብቸኛ የፖለቲካዊ ቅቡልነት አለኝታ ተደርጎ እየቀረበ ነው፡፡ አንዳንዴ ከዚኽም አልፎ፣ ለዴሞክራሲ ዕጦት ሐዘናችን እንደ መጽናኛ ለመቅረብም ይዳዳዋል። ኢኮኖሚያዊ ልማትን የነገሮች ኹሉ ፍጻሜና ማማ አድርጎ ማቅረብ አንዳንዴ በግላጭ፣አንዳንዴም በደፈናው የጊዜያችን ዜማ ኾኗል።
ብሔርም ኾነ ልማት በራሳቸው ዐውድ ውስጥ እስከቆዩ ድረስ መልካም ናቸው፤ ችግሩ ግን ከላይ እንዳልነው፣ የራሳቸው አልበቃ ብሏቸውና ከምሕዋራቸው ወጥተው ሌላውን መጣስና መዋጥ ሲጀምሩ ነው። በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ነገሮችን ኹሉ ከአንድ ነጠላ ዐውድ አንጻር መገንዘብ ተገቢ አይደለም። ለምሳሌ÷ ዐርበኛነትንም ሥነ-ጥበባትንም ባህላዊ እሴቶችንም ጤና ጥበቃንም… ወዘተ ከልማት አጋርነት አንጻር ብቻ መመልከቱ ተገቢ አይኾንም። በምንም ዐይነት ድንጋጌ ዐርበኛነት እና ልማት አንድ አይደሉም። ዐርበኛነት የራሱ ዐውድ አለው፤ ልማትም እንዲኹ። ስለ ዐርበኛነት ሲነሣ የመድፉ ባለሟል ሻቃ በቀለ ወያ ከዐርበኞች መሀል ትዝ ሊሉን ይችላሉ፤ እንዲኹም ስለልማት ሲነሣ አቶ በቀለ ሞላ ትዝ ሊሉን ይችላሉ። ለኹለቱም በየዐውዳቸው ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው ይችላል። ኾኖም የነጻነት ፋኖው በጀግንነቱ፣ የልማት ታታሪውም በታታሪነቱ መወሳት አለባቸው እንጂ ልማትን አውራ እሴት በማድረግ ዐርበኛነትን የልማት ገላጭ ማድረግ የለብንም።
ባለፈው ሥርዐት ዐብዮትን ብቻ የኹሉ ነገር ማማ በማድረግ ጣታችንን ተቃጥለን ነበር። አኹን ደግሞ ብሔር እና ልማት የሚሉ ነጠላ ፅንሰ ሐሳቦችን ብቻ ይዘን፣ እኒኽንም ከኹሉ ነገር በላይ በመስቀላችን፣ በአንድ አገር ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸውን ሌሎች በጎ ነገሮችን እየደፈጠጥን ነው። ኹልጊዜ አንድ ነጠላ ነገርን መርጦ የበላይ ማድረግ፣ የብዙ ዐውዶች ሕብር ልትኾን የሚገባትን ፍትሐዊት አገር ያሳጣናል።
ልማትን በተመለከተ ያለኝ ተጨማሪ ትዝብት፣ አገሪቱ ካለፈው ጊዜ የተሻለ ደረጃ ላይ ናት ሲባል፣ የኢሕአዴግ አቀራረብ የሕዝቡን ታታሪነትና ሥራ ወዳድነት ወደ ጎን በመተው ኹሉን ነገር በራሱ ብቻ እንዳስገኘው አድርጎ ለማሳየት መጣጣሩ ተገቢ አይደለም፡፡ በልማታዊነቱም ቢኾን ከብክነት፣ ከጥራትና ከአድልዎ አኳያ በሦስተኛና ገለልተኛ ወገን ለመፈተሽ ዕድሉ ሳይሰጥ ‹ሠሪው ፈጣሪው እኔ ነኝ› በሚል ፈሊጥ ምንጊዜም የፖሊቲካ ሽልማቱን ለመውሰድ ይሽቀዳድማል፡፡  
‘ፕሮሲጀራል ጀስቲስ’ን በተመለከተ፣ ዕውቅ አስተምህሮ የጻፈው ፕሮፌሰር ስቱዋርት ሃምሻየር (Stuart Hampshire) “ፍትሕ ግጭት ነው” (Justice is Conflict) በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደሚሉት፣ የሰው ልጅ ከጭቅጭቆችና ከግጭቶች ነጻ ባይኾንም፣ ፍትሕ ርትዕ ይሰፍን ዘንድ ኹሉም ወገኖች የሚደመጡበትና ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ሲኖር ነው፤ ካሉ በኋላ፣ የጥንት ሮማውያንን አባባል፣ “የሌላውንም ወገን ድምፅ ስማ” (Audi alteram partam) የሚለውን ምክር ይለግሳሉ።
ለማጠቃለል፣ የዴሞክራሲ መሠረታዊ ግብ የሚሠምረው፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የተለያዩ ሠናያት እና ግቦች ባሏቸው ግልጋሎቶችና እሴቶች በሕዝቡ ተመዝነው ነገሮቹ እርስ በርስ በኩታ ገጠምነት መሔድ የሚችሉበትን ምርጡን መንገድ በነጻነት መምረጥ ሲቻል ነው። ምርጫው በጫና የመጣ ሳይኾን በሕዝቡ ነጻ ፈቃድ የተመረጠ መኾን አለበት፡፡ ይህም የልዩ ልዩ ሐሳቦች ተዋፅኦና ነጻ የአመለካከቶች መንሸራሸርን የግድ ይላል፡፡ ይህን መገደብ ዴሞክራሲንም መገደብ ነው።
በአኹኑ ወቅት በኢሕአዴግ በኩል ሲባል የምንሰማው፣እኛ የምናወጣቸው ፖሊሲዎችና የምናስፈጽማቸው ተግባራት ‘ትክክለኛውን አቅጣጫ’ የተከተሉ ስለመኾናቸው እርግጠኞች ነን፤ የሚል የፍጹማዊነት መርሕ ነው። ይህም በመኾኑ ለተለያዩ አመለካከቶች መንሸራሸር ቦታ ተነፍጓል፤ ለዴሞክራሲ ማበብም ትልቅ መሰናክል ፈጥሯል። ፍጹም እርግጠኛነት የተለያዩ አመለካከቶች መንሸራሸርን የሚገድብ ብቻ ሳይኾን ለዴሞክራሲም ቀንደኛ ጠላት ነው።
በመግቢያው ውስጥ እንደጠቀስኩት ጽሑፌን የማጠቃልለው ለአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በአጭሩ በማቀርበው ‘ግልጽ ደብዳቤ’ ነው።
ይድረስ ለተከበሩ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፤
በቅድሚያ ሰላምታዬ ይድረስዎ እያልኹ በአክብሮት ማስታወሻዬን እጀምራለኹ። እንደ እውነቱ ከኾነ፣ ማስታወሻም ኾነ ደብዳቤ ለእርስዎ ለመጻፍ ሐሳብ አልነበረኝም፡፡ የመጀመሪያ ዕቅዴ ለፕሮፌሰር መርጋ በቃና ትችታዊ ደብዳቤ መጻፍ ነበር። የትችቱም ይዘት በዋናነት የሚያተኩረው፣ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ተነሣ ለተባለው “መከፋፈል” እርሳቸው ከማሸማገል ጀምረው እስከ ውሳኔ አሰጣጥ ድረስ የሔዱበትን መንገድ የተመለከተ ነበር። ኾኖም ግን፣ እርስዎ በፓርላማ ቀርበው ስለዚኹ ጉዳይ በተጠየቁ ጊዜ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናን እና ምርጫ ቦርዱን መሔስና መተቸት በሕግ ሊያስጠይቅ ይችላል፤ ብለው ስላሉ፣ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናን ተችቼ በሕግ ከመጠየቅ፣ አንድ ፊቱን፣ እንደ አንድ ዜጋ፣ ትችቴን ወደ እርስዎ አቅርቤ፣ ሕግ ፊት የሚያስቀርበኝም እንደኾነ፣ በእርሳቸው ሳይኾን በእርስዎ ስም ለመቅረብ መርጬአለኹ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በዴሞክራሲ ሥርዐት ውስጥ፣ “ዐለቀ፣ ፍጻሜውንም አገኘ” ተብሎ የሚዘጋ አንዳችም ፖለቲካዊ ሐሳብና አመለካከት የለም። ኹሉም ፖለቲካዊ እይታዎች ለውይይት፣ ለጥያቄ፣ ለትችትና ለተደጋጋሚ ፍተሻ ኹሌም ክፍት መኾን አለባቸው። ለዚኽ ማሳያ ይኾን ዘንድ፣ አኹን በቅርቡ ከዐርባ ዓመታት በላይ የአሜሪካ የፖለቲካዊ ሳይንስ ክፍል ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረዋል ከሚባሉ ጥቂት ምሁራን መካከል አንዱ የኾኑት ፕሮፌሰር ሮበርት ዳል (Robert Dahl) ስለ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የጻፉትን ትንሽ እጠቅስ ዘንድ ይፈቀድልኝ።
ፕሮፌሰሩ፣ ‘’የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ምን ያኽል ዴሞክራሲያዊ ነው?’’ (How Democratic is the American Constitution?) በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች አቅርበዋል።
አንደኛ፣ ዐሥራ አንድ ስቴቶች እና ሠላሳ ዘጠኝ እንደራሴዎች ብቻ ከዛሬ ኹለት መቶ ዓመታት በፊት ያረቀቁትንና የፈረሙትን ሕገ መንግሥት ዛሬ ለምን እንቀበላለን? እውን፣ አብዛኞቹ አሜሪካውያን እንደሚሉት፣ ሕገ መንግሥቱን የምንከተለው የዜጎችን ኹሉ ቅቡልነት ስላገኘ ነውን? ብለው ይጠይቁና ምላሹን ለማግኘት ሌላ ጥረት ሳያስፈልጋቸው፣ ግን እስኪ፣ ይህን መጽሐፍ ከምታነቡ ዜጎች መካከል ምን ያኽላችሁ ለሕገ መንግሥቱ ቅቡልነትን ትሰጡ ዘንድ ተጠይቃችኹ ሰጥታችኋል? ሲሉ ይሞግታሉ።
ኹለተኛ፣ አንዳንድ አሜሪካውያን፣ የምንከተለው ሕገ መንግሥት ከዓለም ምርጡ ነው፤ ብለው እንደሚናገሩ ፕሮፌሰሩ ያወሱና ይህ አባባል እውነት ከኾነ፣ ለምን ኻያ ሦስት የዓለም ታላላቅ ዴሞክራሲዎች የአሜሪካን ሕገ መንግሥት ነጥብ በነጥብ አልገለበጡም? ሲሉም ይጠይቃሉ። የፕሮፌሰር ሮበርት ዳል ዋነኛ ዓላማ፣ የአሜሪካ ሕገ መንግሥትን ማስቀየር ሳይኾን፣ ሕዝቡ ስለ ሕገ መንግሥቱ ያለውን ዶግማዊ አመለካከት ሽሮ ዳግም ወደ ውይይትና ፍተሻ ይገባ ዘንድ ለመጎትጎት ነው። ኹለት መቶ ዓመታት የሞላውና በዓለም ላይ አድናቆትን ያተረፈው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ጥያቄና ትችት የሚቀርብበት ኾኖ ሳለ፣ ኻያ ዓመታት ብቻ ያስቆጠረው የአገራችን ሕገ መንግሥት ላይ ጥያቄ በሚነሣ ጊዜ፣ ሕገ መንግሥቱን “ለማፍረስ (ለመናድ)” በሚል ፈሊጥ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ ውይይት የሚያደርጉባቸው መንገዶች መዘጋት የለባቸውም።
ከላይ ፕሮሲጀራል ጀስቲስን በተመለከተ እንደጠቀስነው፣ እንደ እርስዎ በከፍተኛ የአገር መሪነት ቦታ ላይ የተቀመጠ ሰው የአንድ ወገንን ድምፅ ብቻ ሳይኾን፣ የሌላውንም ወገን አመለካከትና ስሞታ ማድመጥ እንደሚኖርበት ያውቃሉ የሚል እምነት ቢኖረኝም፣ አንድነት ፓርቲን በተመለከተ በፓርላማ ቀርበው የሰጡት አስተያየት ይህንኑ በተግባር አላሳየኝም። ይህም የኾነው በአንድ በኩል፣ ትክክለኛ መረጃ ስላልደረስዎ ሊኾን ይችላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሌላውን ወገን ስሞታ ለመስማት ተገቢውን አትኩሮት ስላልሰጡ ሊኾን ይችላልና እንደ አንድ ዜጋ ቅሬታ አድሮብኛል።
በአንድ አገር ውስጥ ኅብረተሰባዊ ሒስ ከተከለከለና መንግሥት ነጠላ አመለካከትን አንግሦ ሌላ ተፃራሪ ሐሳቦችን ሳያስተናግድ ከሔደ፣ የዴሞክራሲ ጎዳና ተብሎ የተሰየመው በስም ብቻ ኾኖ ፍሬ ሳያፈራ ይመክናል። ከእርስዎና ከአመራሩ ክፍል፣ አገሪቱ በሕዳሴ ጎዳና ላይ እንደምትገኝ በተደጋጋሚ ተነግሮናል። ኾኖም ግን፣ እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ ከዚኽ ቀደም የሠመረ ሕዳሴ ያካሔዱ አገሮች በሙሉ ሕዳሴንና ትችትን በመነጣጠል ሳይኾን በአንድነት ይዘው የዘለቁ ናቸው። ይህም የሚኾንበት ምክንያት፣ የሕዳሴ ፅንሰ ሐሳብ በራሱ ትችትን አካትቶ የያዘ ፅንሰ ሐሳብ ነው።
ለማጠቃለል፣ እርስዎ ጠቅላይ ሚኒስትር በኾኑ ጊዜ በኹለት ጉዳዮች የተነሣ ብዙ ኢትዮጵያውያን ደስ ብሏቸዋል፡፡ ይኸውም አንደኛ፣ እርስዎ የተገኙበት የፖለቲካ ምኅዳር ኢትዮጵያን በሚመለከት “ሐምሌታዊ ጭቅጭቅ” (የመኾን አለመኾን አተካራና ውልውል) ከሌለበት ክፍል በመኾኑ፤ ኹለተኛ፣ እርስዎ ጠመንጃ ታጥቀው ወደ ሥልጣን የመጡ ባለመኾኑ፣ አገሪቱ ልታደርግ ለሚገባት የሲቪል አስተዳደር ሽግግር መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ተብሎ በመታሰቡ ነው። ኾኖም ግን፣ ሕዝብ በእርስዎ ላይ ያሳደረው ይህ በጎ አመለካከት እንዳይመክን ተጠሪነትዎ ለአንድ ፓርቲ ሳይኾን፣ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነትዎ ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ መኾኑን ምንጊዜም ባይዘነጉ የሚል ማዘከርያ(ማስታወሻ) አለኝ።
ክቡርነትዎ መዘንጋት የሌለበት፣ ከዚኽ ቀደም በዐድዋ፣ በማይጨው እና በባድመ ከወራሪ ጠላት ጋር ተናንቆ ሉዓላዊነቱን ያስከበረው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ በሌላ በየትኛውም ክፍል ቢኾን የተዋደቀውም አገሬ ተደፈረች በማለት እንጂ ውለታ ለማስቆጠር አልነበረም፡፡ ካለፈው ሥርዐትም ጋር ቢኾን መገዳደሉ ከእርስ በርስ ጦርነት የተነሣ እንጂ አንዱ የኢትዮጵያ ክፍል ከሌላው ኢትዮጵያዊ ካሳ የሚጠይቅበት ጉዳይ ኾኖ አይደለም፡፡ በሌላው ዓለም በቅርቡ የተካሔዱት የእርስ በርስ እልቂቶች (ከአሜሪካ እስከ ስፔን) የሚያረጋግጡትም ለጉዳቱ የጋራ መፍትሔ ማበጀትን እንጂ የአንዱ ከሌላው የበደል ካሳ መጠየቅን አይደለም፡፡
ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም፣ ያለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹ኢትዮጵያዊ›› እንዲኾኑ የብዙ ሰው ጸሎትና ተማጥኖ ነበር፡፡ እርስዎ ደግሞ እውነተኛ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር›› እንዲኾኑ ምኞታችን ነው፡፡ በመኾኑም ክቡርነትዎ ምልዓተ ሕዝቡ የሚፈልገውን እንዳይኾኑ መሰናክሎች ቢበዛብዎትም ጫናውን ተቋቁመው የብዙኃኑ ተምኔት ይደርስ ይፈጸም ዘንድ እመኛለኹ፡፡
ከፍ ካለ አክብሮትና ምስጋና ጋር

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከሦስት ዐሥርት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በሚሌኒየሙ መባቻ ወደ አገራቸው ተመልሰው ላለፉት ሰባት ዓመታት በማስተማር ሥራ ላይ ቆይተዋል፡፡ ምሁሩ በዋናነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ቢኾኑም በሕግ ፋክልቲ፣ በሴንተር ፎር ሂዩማን ራይትስ፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ በአምስት ኪሎ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋክልቲ፣ በቴአትሪካል አርትስና በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤትም አስተምረዋል፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በተጠቀሱት የትምህርት መስኮች በተለያየ ጊዜ ሲያስተምሩ ቢቆዩም ከጠየቁት የዓመት ዕረፍት (sabbatical leave) ጋር ተያይዞ ከዩኒቨርስቲው መሰናበታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  አዲስ አድማስ ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋር ተከታዩን አጭር ቃለምልልስ አድርጓል፡፡

    በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በእርስዎ መካከል ምንድን ነው የተፈጠረው?
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ጋር በኹለት ጥያቄዎች ዙሪያ የማይታረቅ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ በመጀመሪያ የዩኒቨርስቲው የሴኔት ሕግና የቅጥር ውሌ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው÷ አንድ መምህር ለስድስት ዓመት በተከታታይ ከአስተማረ፣ ለአገለገለበት ዘመን የአንድ ዓመት የጥናትና ምርምር ዕረፍት (sabbatical leave) እንደሚሰጠው ተደንግጓል፡፡ ኾኖም ግን ዩኒቨርስቲው ‹‹የጡረታ ሥርዓተ - ሒደቱን አላሟላኽም›› በሚል በሕጉ ፊት የማይጸና ሰበብ ፈጥረው ይገባኻል ብለው ከፈቀዱልኝ በኋላ መልሰው ነጥቀውኛል፡፡ ለማንኛውም መምህር ሥርዓተ ሒደቱን የማስፈጸም ሓላፊነት የሰው ሀብት አስተዳደሩ ድርሻ ኾኖ ሳለ፣ እኔን ተጠያቂ ማድረጋቸው ብዙዎችን አስገርሟል::
በነገራችን ላይ የጥናት ዕረፍት ፈቃዴን የጠየቅኹት ከሦስት ዓመት በፊት፣ ስድሳ ዓመት ሳይሞላኝ ነበር፡፡ በየሰበቡ ሲጓተት ስለቆየ ወደ ስድሳ ዓመቱ ገደብ ደረስኹ፡፡ ጉዳዩ ወደ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ከመሔዱ አስቀድሞ ውስጣዊ ተቋማዊ መፍትሔ ለማበጀት ወደ ዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ቀርቦ ምላሽ ስጠባበቅ ከሦስት ወራት በላይ ተቆጥረዋል፡፡
የሥራ ውሌን በተመለከተ፣ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል የእኔን የአገልግሎት ቆይታ እንደሚፈልግና በተለይም በቅርቡ ለሚጀምረው የሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ተሳትፎዬ እንደሚጠቅም በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ በመወሰኑ ውሌ እንዲራዘም ለማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ኮሚሽን ጽፎልኝ ነበር፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሓላፊዎች በተሰበሰቡበት፣ ኮሚሽኑ ጉዳዩን በአጀንዳ ይዞ ከተወያየበት በኋላ የፍልስፍና ትምህርት ክፍሉን ጥያቄ ዳግመኛ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶበት፣ ውሳኔው በማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኑ በፕ/ር ወልደ አምላክ በዕውቀት በኩል የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ይኹንታቸውን እንዲሰጡበት(እንዲያጸድቁት) ተጠይቆ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ግን ከአራት ወራት ያኽል ቸልተኝነት በኋላ ‹‹ወረቀቱ ይመጣለታል›› በሚል ለተከታዩ ሴሚስተር እንዳልደለደል በአዲሱ ዲን በኩል ለትምህርት ክፍሉ ሊቀ መንበር መመሪያ አስተላለፉ፡፡ መመሪያው የእኔን መሰል ጥያቄ ባቀረቡ ሌሎች መምህራን ላይም የተላለፈ ነበር፡፡ ከሦስት ወራት በላይ ደመወዜን ይዘው መክፈል ከአቆሙ በኋላ ‹‹ለሚመጣው ሴሚስተር አትመድቡት›› ማለት በአካዳሚያ ቋንቋ ግለሰቡ ተሰናብቷል ማለት ነው፡፡
በመሠረቱ፣ የትምህርት ክፍሌና አካዳሚክ ኮሚሽኑ የሥራ ውሌን መራዘም ተስማምተው ላቀረቡት ጥያቄ ሲኾን እንደወጉ ማጽደቅ አልያም በአስቸኳይ ውሳኔን ማሳወቅ ሲገባ፣ ፕሬዝዳንቱ ከሦስት ወራት በላይ ማቆየታቸው ኢ-ሕጋዊ ነው፤ ሕጉን ጠብቆ በወጉ ለቀረበ ጥያቄ ከሦስት ወራት በላይ ምላሽ አለመስጠት እብሪት፣ ትዕቢትና ማናለብኝነት እንጂ ሌላ ሊኾን አይችልም፤ በተመሳሳይ ወቅት አንድ ዐይነት ጥያቄ በደብዳቤ ከአቀረብነው መምህራን መካከል፣ ለምሳሌ ከኛው ትምህርት ክፍል ዶ/ር በቀለ ጉተማ በሥራው እንዲቀጥል በቃል ትእዛዝ ፈቅደው፣ ለእኔ በአግባቡ ውሳኔ ሳይሰጡ ‹በሚቀጥለው ሴሚስተር እንዳትመድቡት’ ማለት የአድልዎ አቀራረብ ብቻ ሳይኾን በዘፈቀደና በግፊት የሚካሔድ አመራር መኾኑን ያረጋግጣል፡፡ በሌላ በኩል፣ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አድማሱ ዩኒቨርስቲውን ለመምራት ያላቸውን ብቃት ከዚህ ቀደም በአደባባይ ስለጠየቅኹ በቂም በቀልና ኹን ብለው እኔን ለመጉዳት የደረሱበት ውሳኔ ነው፡፡
የጥናትና ምርምር ዕረፍት(sabbatical leave) በተመለከተ በጊዜው የኮሌጁ ዲን የነበሩት ዶ/ር ገብሬ ይንቴሶ፤ የፕሬዝዳንቱን ፍላጎት ተከትለው ከላይ እንደጠቀስኹት የሰጡኝን ፈቃድ መልሰው ነጥቀውኛል፡፡ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ከማምራቴ በፊት፣ የፕሬዝዳንቱን ምላሽ ከወዲኹ ባውቀውም አቤቱታዬን የግድ ለእርሳቸው ማቅረብ ነበረብኝ፡፡
በኮሌጁ የቀድሞ ዲን ውሳኔ ላይ ከዐሥር ገጽ ያላነሰ አባሪ ሰነዶች አያይዤ ጠዋት ላቀረብኹት አቤቱታ፣ ከቀትር በኋላ ‹‹በጥልቅ መርምረን›› በሚል በአንድ መሥመር የኮሌጁ ውሳኔ እንደማይሻር የሚገልጽ ፌዝና የቀልድ ምላሽ ነው የተሰጠኝ፡፡ ይህ የሚያሳየው ፕሬዝዳንቱ ለዩኒቨርስቲው መምህራን ከበሬታ የሌላቸውና አመራራቸውም ከሞራላዊነት የተራቆተ መኾኑን ነው፡፡ እኔ ግን ታዋቂው አርበኛ አበበ አረጋይ በአንድ ወቅት በፋሽስት ጣልያንና በባንዳ ለተከቡበት የተራቡ ጭፍሮቻቸው ‹‹ሞተን አንጠብቃቸውም፤ ተረጋግታችኹ ብሉ›› እንዳሉት፣ ከማባረር ያልተናነሰ የዘገየ አንድ ብጣሽ ወረቀት ገና ለገና ይመጣል ብዬ ሞቼ አልጠብቃቸውም፡፡
ከዚህ ቀደም የጡረታ ጊዜያቸው ደርሶ ለማራዘም የተፈቀደላቸው መምህራን አሉ ? ማለትም በዩኒቨርስቲው አሠራር የጡረታ ጊዜያቸው የደረሰ መምህራን ውላቸውን ማራዘም ይችላሉ?
በተለምዶ ስድሳ ዓመት የሞላቸው መምህራን የውል ማራዘሚያ ጊዜ ይጠይቃሉ፡፡ እኔ የማውቃቸውና በተደጋጋሚ የተጨመረላቸው መምህራንም አሉ፡፡ በጣም አስገራሚና በግቢው አነጋጋሪ የኾነው የእኔና የዶ/ር መረራ ጉዲና የውል ማራዘሚያ ጊዜ መከልከሉ ነው፡፡
ግን የዚህ ኹሉ መነሻ ምንድን ነው ብለው ይገምታሉ?
ከኹሉ በፊት የእኔ መከልከልና መሰናበት ከፖሊቲካ እይታ አኳያ የመነጨ መኾኑ የታወቀ ነው፡፡
ማለት…
በዩኒቨርስቲው በማስተማር ሥራ በቆየኹባቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት፣ በጽሑፍና በተለያዩ መድረኮች የማደርጋቸው የዐደባባይ አእምሯዊ እንቅስቃሴዎች አልተወደዱም፡፡ እንዲያውም ለሹመኞች ቅርበት ያላቸው አንዳንድ ወዳጆቼ እንዳጫወቱኝ፣ ‹‹ዳኛቸው፣ ዩኒቨርስቲውን እንደ ደጀንና ገዥ መሬት ተጠቅሞ መድፍ ሲተኩስብን ቆይቷል›› ተብዬአለኹ፡፡ በርግጥ ይህ ዓይነቱ አቋም ከተወሰደ በኋላ በሥራ ገበታዬ እንድቀጥል አለመደረጉ አይገርመኝም፡፡
ከዩኒቨርስቲው በዚኽ መልኩ ሲሰናበቱ ምን ተሰማዎ?
እንደ እውነቱ ከኾነ የተደበላለቀ ስሜት ነው በውስጤ የተፈጠረው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህ ነገር ከሰባት ዓመት በኋላ መኾኑ አስደስቶኛል። ይኸውም የመጣኹበትን የማስተማር ዓላማ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር በመኾን ለመስኩ ተተኪና ምሉዕ የኾኑ ተማሪዎች ለማፍራት በመብቃታችን አስደስቶኛል፡፡ ይህ ክልከላና ስንብት በቂ ምሩቃን ባላፈራንበት ከሦስትና ከአራት ዓመት በፊት ቢከሠት ኖሮ አዝን ነበር፡፡ በኹለተኛ ደረጃ፣ ‹የዓመት ዕረፍት(ሳባቲካል) አይሰጥኽም፤ ከእንግዲኽ ማስተማርም አትችልም› ስባል ለራሴ በጥልቀት ተሰምቶኝ ያልኹት፣ ‹‹አኹን ገና ኢትዮጵያዊ ኾንኩ፤ ኢትዮጵያዊ ማለት መብቱ የሚረገጥ ማለት ነው›› የሚል ነበር፡፡ በዚኽ ሰባት ዓመት ቆይታዬ ከአሜሪካ ሳልፈታ ይዠው የመጣኹት የነፃነትና የመብት አቅዋም፣ ከአገራችን ፖሊቲካዊ ነባራዊ ዕቀባ በተፃራሪው እንደ ልቤ እንድተችና ያለገደብ እንድናገር አስችሎኝ ነበር፡፡ አኹን ግን ሥርዓቱ ‹ይኼ አሜሪካ አይደለም፤ እንደ ጎረቤትኽ ሳይኾን እንደቤትኽ እደር› ብሎኛል፡፡ ይህን ስል ግን፣ እኔ በዕድሜዬ የምወልዳቸው ልጆች በኾነ ባልኾነ ክሥ ወኅኒ ቤት ተወርውረው ባሉበት ኹኔታ ከሥራ አባረሩኝ ብዬ የማለቅስ ሰው አይደለኹም፡፡ በእኒኽ ብሩህ ተስፋ ባላቸው ወጣቶች ላይ ከደረሰው አንጻር ሲታይ መብቴ መረገጡ እውነት ቢኾንም፣ የአገራችን ተረት ‹‹እናቱ ውኃ ልትቀዳ የወረደች ልጅና እናቱ የሞተችበት ልጅ አንድ ጋር ቆመው ያለቅሳሉ›› እንደሚባለው ይመስልብኛል፡፡
በመጨረሻም በአንድ በኩል፣ በውጭ ለብዙ ዓመት ቆይቼ ስመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የት ከረምክ ሳይለኝ፣ ችሎታዬ በሚፈቅድልኝ ቦታ ሥራ ሰጠኝ፡፡ ለዚኽ ትልቅ ምስጋና ነው የማቀርበው፡፡ ኾኖም በሌላ በኩል የውስጥ አስተዳደሩና የውጭ የፖሊቲካ ኃይሎች በመተባበር መክረው ከሕዝብ ባገኘኹት ቸርነት ላይ ወይነውብኛል!
ከዚኽ በኋላስ ምን ዓይነት ሥራ ላይ ለማተኮር ያስባሉ?
ይህን ጥያቄ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ባለበት አገር ብትጠይቀኝ ኖሮ፣ ጉዳዩ በራሴ የሚወሰን በመኾኑ አኹኑኑ እመልስልኽ ነበር፤ ነገር ግን እንደ ቤትኽ እደር ተብዬአለኹና የጥያቄው ምላሽ በእኔ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ እንዲያውም ጥያቄው በአንድ ወቅት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሉ የተባለውን ያስታውሰኛል፡፡ አንድ ሹም ጃንሆይ ፊት ቀርበው የንጉሡ ትችትና ተግሣጽ ሲገጥማቸው፣ ‹‹እንዲያውም ግርማዊ ሆይ፣ የሰጡኝ ሹመት ይቅርብኝ፤ የአባቴን ርስት እያረስኩ እኖራለኹ›› አሏቸው፡፡ ጃንሆይም ወዲያው ‹‹እርሱንም እኛ ስንፈቅድ ነው…›› አሉ ይባላል፡፡
እኔም እንደ አቅሜ ለመሥራት ፍላጎት ቢኖረኝም፣ በቀጣይ ምን መሥራት እንደምችልና እንደማልችል ብያኔው በመሠረቱ ከእኔ ውጭ ነው፡፡ በተቻለኝ መጠን ግን በአለችኝ ቀሪ ዕድሜ አገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡ በዚኹ አጋጣሚ በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኝበትን ተቋማዊ ኹኔታ በተመለከተ አንድ ጽሑፍ እንደማቀርብ ከወዲኹ ለማሳወቅ እወዳለኹ፡

ከ97 ዓ.ም በፊት በተለያዩ የግል ጋዜጦች ላይ በሪፖርተርነትና በዋና አዘጋጅነት ሲሰራ እንደነበር የሚናገረው ጋዜጠኛ አለማየሁ ባዘዘው፤ ጋዜጦቹ ሲዘጉ የራሱን መፅሄት ለማሳተም እንደሞከረም ይገልፃል፡፡ “ጊዜያችን” የተሰኘች መፅሄት ለማሳተም ፈቃድ ጠይቆ ለ10 ወር ያህል ሳይሰጠው ለቢሮና ለሰራተኛ እየከፈለ በኪሳራ መቆየቱንና የገንዘብ አቅሙ ከተዳከመ በኋላ ፈቃዱን እንዳገኘ የሚናገረው ጋዜጠኛው፤ መጽሄቷ በገንዘብ እጥረት ከሶስት እትም በላይ መዝለቅ እንዳልቻለች ይገልፃል፡፡ የጋዜጠኝነት ህይወቱ በአሳታሚዎች መምጣትና መሄድ ላይ የተንጠላጠለ እንደነበር የገለጸው አለማየሁ፤ ከጋዜጠኝነት ሥራው ጋር በተያያዘ በየጊዜው ሲታሰርና ሲፈታ መቆየቱንም ይናገራል፡፡ የማታ ማታ አብዛኞቹ የሥራ ባልደረቦቹ ከአገር ቢሰደዱም እሱ ግን እዚሁ ከጋዜጠኝነት ሙያው ተለይቶ የፕሮሞሽን ስራዎችን እየሰራ እንደሚኖር ገልጿል፡፡   
“አትኩሮት” የተሰኘች ጋዜጣ በ1991 ዓ.ም ማሳተም የጀመረው ታምራት ዙማ፤ በ1993 ዓ.ም “መንግስት ለመገልበጥ አሲረሃል” የሚል ይዘት ባላቸው አራት ክሶችና ፍቃድ ከማሳደስ ጋር የተያያዙ 2 ክሶች ቀርበውበት ለእስር በመዳረጉ የሁለት አመት እድሜ ብቻ የነበራት ጋዜጣው ከገበያ እንደወጣች ያስታውሳል፡፡ በመጨረሻም በአምስቱ ክሶች ነፃ ሆኖ ፍቃድ ባለማሳደስ በሚለው ብቻ የ2ሺህ ብር ቅጣት እንደተጣለበት ይገልጻል፡፡ ከ11 ወራት እስራት በኋላ ከማረሚያ ቤት ሲወጣ ጋዜጣዋን መልሶ ለመጀመር ቢፍጨረጨርም በተለያዩ ምክንያቶች  እንዳልተሳካለት የጠቆመው ጋዜጠኛው፤ ከብዙ ዓመታት በኋላ በ2006 ዓ.ም “አፍሮታይምስ” ጋዜጣ ላይ መስራት እንደጀመረ ይናገራል፡፡ ሆኖም ግን ይሄኛው ጋዜጣም ብዙ ሳይቆይ በፍ/ቤት ክስ ተመስርቶበት በመዘጋቱ በአሁኑ ሰአት ከሚወደው ሙያ ተነጥሎ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያነት እየሰራ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡ አብረውት ይሰሩ ከነበሩ ዘጠኝ ጋዜጠኞች መካከል ግማሾቹ ከአገር መሰደዳቸውን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከጋዜጠኝነት ውጭ በሆኑ ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡ “ፕሬሶች ለመንግስት መስታወት ናቸው” የሚለው ጋዜጠኛው፤ መንግስት ለነፃው ፕሬስ ማበብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ቢያደርግ ተጠቃሚው ራሱ ነው ይላል፡፡
የኢዮብ አሳታሚ ድርጅት ባለቤት የነበረው ኢዮብ ደመቀ፤ ሐምሌ 1986 ዓ.ም የተመሰረተችውን “ታሪክ” ጋዜጣን ጨምሮ “አንደበት” እና “ወቅት” የተሰኙ ጋዜጦችን ያሳትም ነበር፡፡ ጋዜጦቹ መዝለቅ የቻሉት ግን እስከ 1994 ዓ.ም ብቻ ነው፡፡ ለጋዜጦቹ መዘጋት ምክንያት የሆነው ደግሞ የክሶች መብዛት እንደነበረ ያስታውሳል፡፡ “በአዘጋጅነቴና በአሳታሚነቴ ወደ 32 የሚደርሱ ክሶች ተመስርተውብኝ ነበር” የሚለው ኢዮብ፤ የክሶቹ መብዛት የጋዜጦቹን ስራ አስተጓጉሎ በአጭሩ ቢቀጨውም በፍ/ቤት የተላለፈብኝ ቅጣት ግን አልነበረም ብሏል፡፡
“ታሪክ” ጋዜጣ ላይ ይሰሩ ከነበሩት ጋዜጠኞች ውስጥ ከፊሎቹ ከሃገር መሰደዳቸውን፣ ቀሪዎቹ እዚሁ አገር ውስጥ በሌላ የሥራ መስክ ተሰማርተው እንደሚገኙ የሚናገረው ኢዮብ፤ በአሁን ሰዓት ያለምንም ስራ ቤት ውስጥ ተቀምጦ በቤተሰቦቹ ድጋፍ እንደሚኖር ገልጿል፡፡ በወቅቱ የተመሰረቱበት ወደ 32 የሚጠጉ ክሶች “ሃሰተኛ ወሬ በማናፈስ” የሚል ይዘት ያላቸው እንደነበሩ የሚያስታውሰው ኢዮብ፤ “በተለይ ስለ ሻዕቢያ በተሰራ ዘገባ ርዕስ ላይ ትምዕርተ ጥቅስ ባለመጠቀም የሚል “አስቂኝ” ክስ ቀርቦብኝ ነበር” ይላል፡፡ “ጋዜጣውን ወደ ሰፊ የመፅሄትና የጋዜጣ ኢንዱስትሪ የማሳደግ ህልም ነበረኝ” የሚለው  ኢዮብ፤ “ያ ህልሜ መጨናገፉን ሳስብ ስሜቴ ክፉኛ ይጎዳል፡፡” ብሏል፡፡
  የግል ፕሬስ አለ ወይስ የለም?
በአሁኑ ወቅት የሚታተሙትን ጥቂት የግል ፕሬስ ውጤቶችና ዝቅተኛ የስርጭት መጠናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የግል ፕሬስ የለም ብለው የሚከራከሩ ወገኖች ያሉትን ያህል የግል ፕሬስ መኖር የሚለካው በቁጥር አይደለም በሚል “ፕሬስ ድሮ ቀረ” የሚለውን የማይቀበሉ ወገኖች አሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ ከ97 በፊት “የሀገሪቱ የፕሬስ ኢንዱስትሪ ወርቃማ ጊዜ ነበር፣ ነገር ግን ፕሬስ ድሮ ቀረ በሚለው አልስማማ” ይላሉ፡፡ “በወቅቱ የነበሩት ፕሬሶች ብዛት ቢኖራቸውም መረጃን ከጋዜጠኝነት ሙያ አንፃር በጥራት ማቅረብ ይጐድላቸዋል፤ ገለልተኝነትም አልነበራቸውም” ያሉት ምሁሩ፤ “አብዛኞቹ በሙያው ሥነምግባር የማይመሩ ፣ የርዕዮተ አለም አቀንቃኞችና ተመሪዎች ነበሩ” ብለዋል፡፡  
ፖለቲከኛው አቶ ሙሼ ሰሙ ግን ከምሁሩ ሃሳብ ጋር አይስማሙም፡፡ “ጋዜጦች የርዕዮተ አለም ደጋፊዎች ሆነው መስራታቸው በሠለጠኑትና የሚዲያ ምህዳራቸው አድጓል በሚባሉት አሜሪካን በመሳሰሉ ሀገራትም የሚታይ ነው የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ከዲሞክራቶችና ከሪፐብሊካኖች ጋር ወግነው የሚሠሩ ጋዜጦች እንዳሉ በመጥቀስ፣ እንደውም የኛ ሀገር ፕሬሶች ቀጥተኛ ወገንተኝነት አይታይባቸውም ይላሉ፡፡
የግል ፕሬሶች ቁጥር መቀነስ ብቻ በአገሪቱ ነፃ ፕሬስ የለም ለማለት አያስደፍርም የሚሉት ዶ/ር ነገሪ፤ ዋናው ብዝሃ ሃሳብን የማንሸራሸር አቅማቸውና የዘገባቸው ጥራት ነው ሲሉ አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡ “የኔም ጥናት ሆነ ሌሎች ያነበብኳቸው ጥናቶች ጋዜጠኞቻችን ሃላፊነት መውሰድ ላይ ጉድለት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ ያሉት ምሁሩ፤ ይሄ ግን ባለሙያዎቹ የጋዜጠኝነት እውቀት ይጐድላቸዋል ማለት አይደለም፤ በአግባቡ እውቀታቸውን አይተገብሩም፤ ይህም በገለልተኝነት እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል” ብለዋል፡፡ ጋዜጦች ቁጥራቸው ለምን እንደተመናመነ ሲያስረዱም፤በገበያው ተወዳዳሪ ለመሆን አለመቻል፣ የሥርጭት ስልታቸው የተጠናከረ አለመሆንና ከሙያው ሥነ ምግባር ውጭ ሲንቀሳቀሱ በህግ ተጠያቂ ሆነው ከስርጭት መውጣታቸውን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። እንዲያም ሆኖ የግል ፕሬስ አለ ወይም የለም የሚያሰኘው የጋዜጦች ቁጥር መብዛትና ማነስ አይደለም ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤ በዋናነት መታየት ያለበት ብዝሃ ሃሳብን የማንሸራሸር አቅማቸውና የዘገባቸው ጥራት ነው ሲሉ ያሰምሩበታል፡፡  
አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ “ጋዜጦች የሉም ለማለት ያዳግተኛል” ይላሉ - ለበርካታ አመታት ሳይቋረጡ የዘለቁ በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጦች እንዳሉ በመጥቀስ፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ለታየው የግል ፕሬሱ መውደቅ መነሣት የመንግስት ጫና ትልቁን ድርሻ ይይዛል ያሉት አቶ ሙሼ፤ የማህበረሰቡ የንባብ ባህልና መረጃን ከጋዜጦች ለማግኘት ያለመሻትም ሌላው ችግር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የፕሬስ ነፃነት ሲታወጅ ወደ ጋዜጣ ኢንዱስትሪ የገባው የህብረተሰብ ክፍል በፖለቲካ የተሸነፈው ሃይል መሆኑም ሙያዊ ዝንባሌው በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሆንና ስሜታዊነት እንዲጎላ አስተዋጽኦ ማድረጉን ለፕሬሱ መቀጨጭ እንደ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ፕሬሶቹ በመንግስት የሚሰነዘርባቸው ከፍተኛ ወቀሳ አሳማኝ አይደለም የሚሉት ፖለቲከኛው፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተግባራዊ ሲደረግ መንግስት ምን ድጋፍ አድርጓል?” ሲሉ ይጠይቃሉ - ጋዜጠኞቹ በራሳቸው ተነሣሽነት በገባቸው ልክ መብቱን ለመጠቀም ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን በመጠቆም፡፡ ፕሬሱ በተወለደ ማግስት እንዲጎለምስ መጠበቅ ትክክል አይደለም ያሉት አቶ ሙሼ፤ “እንኳን ፕሬሱ ኢህአዴግም ላለፉት 23 አመታት ዲሞክራሲን ለመገንባት ገና ጊዜ ያስፈልገኛል እያለ ነው” ብለዋል፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህርና በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉት አቶ እንግዳወርቅ ታደሠ፤ ከደርግ ውድቀት ማግስት ጀምሮ እስከ 1998 የነበረው የሃገሪቱ ፕሬስ የተለያየ መልክ ውስጥ ያለፈ ነው ይላሉ - በሙያ ረገድም ብዙ እንከኖች እንደነበሩበት በመጥቀስ፡፡ ከ1998 ዓ.ም በኋላ ግን ሙያቸው የጎላ እንደ “አዲስ ነገር” ያሉ ጋዜጦች መምጣታቸው የደበዘዘውን የጋዜጣ ኢንዱስትሪ አነቃቅቶት ነበር፤ ሆኖም ጋዜጦቹ በተለያየ ምክንያት እየተንጠባጠቡ ከገበያ መውጣታቸው የግል ፕሬሱን እንዳደበዘዘው መምህሩ ይገልፃሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ አሁንም ያሉት ጋዜጦች  መረጃን የማዳረስ አቅም የሚናቅ አይደለም ብለዋል፡፡
የጋዜጣ ባለቤቶች የኢኮኖሚ አቅም፣ የሙያ ስነምግባር ጉድለቶች፣ ዜናና ዘገባዎች አዲስ አበባ ተኮር መሆናቸው እና የመሳሰሉት የግሉ ፕሬስ ተግዳሮቶች ናቸው የሚሉት መምህሩ፤ በየጊዜው መንግስት የሚፈጥረው ጫናም ለፕሬሱ መሰናክል ከመሆን አንፃር የማይናቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ የመረጃ ማግኛ ዘዴዎችን ማስፋት አለመቻልም ሌላው የፕሬሱ ችግር ነው ይላሉ መምህሩ፡ ይሁን እንጂ ፕሬሱ ጨርሶ ጠፍቷል የሚለውን አስተያየት እንደማይቀበሉ የገለፁት አቶ እንግዳወርቅ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመኑና ተደራሽነታቸው እየጠበበ ቢሆንም የአቅማቸውን የሚኳትኑም እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ያለው እውነታ ከግል ፕሬሱም የባሰ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ በግል ሬዲዮ ከአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ወደ ኋላ ቀርተናል የሚሉት ምሁሩ፤ የግል ቴሌቪዥን እስከዛሬ አለመኖሩና ላለመኖሩ የሚሠጡት ምክንያቶች እምብዛም አሣማኝ አይደሉም ባይ ናቸው፡፡  
አለማቀፍ የህግ ባለሙያውና ፖለቲከኛው ዶ/ር ያዕቆብ ሃይለማርያም በበኩላቸው፤ የግል ፕሬሶች የሉም ለማለት ባያስደፍርም ጋዜጠኞችና ፕሬሶች ከባድ ጫና እንዳለባቸው አውቃለሁ ይላሉ፡፡ ፕሬሶች መስዋዕትነት ከፍለዋል ብለው እንደሚያምኑ የጠቆሙት የህግ ባለሙያው፤ በአለማቀፍ ደረጃ ከኢራን ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች በስደትና በእስራት ተጠቃሽ እንደሆኑ አለም ሁሉ የሚያውቀው ነው ይላሉ፡፡
የኢህአዴግ ጽ/ቤት የህዝብና ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው፤የግል ፕሬስ መሠረታዊ ችግር መንግስት ቁጥጥር ማድረጉና  እርምጃ መውሰዱ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ “የግል ፕሬሱ ችግር የህብረተሰቡን ፍላጐት ያገናዘበ መረጃ ይዞ አለመውጣቱ ነው” ባይ ናቸው፡፡  
መንግስት ምርጫን አስታኮ የግል ፕሬሶች ላይ እርምጃ ይወስዳል የሚለውን ውንጀላም አይቀበሉም፡  “በአጋጣሚ ባለፈው አመት እርምጃ የተወሰደባቸው ፕሬሶች አስቀድሞ ተደጋጋሚ ምክር የተሰጣቸው ቢሆንም የተሠጣቸውን ምክር ወደ ጐን ገፍተው በመጓዛቸው ለህዝቡ ጥቅም ሲባል መልክ ለማስያዝ ተሞክሯል” ብለዋል፡፡
በአለም ላይ “መንግስትን እቀይራለሁ፣ አጠፋለሁ” የሚል ሚዲያ የለም ያሉት አቶ ደስታ፤ የእነዚህ ፕሬሶች አካሄድ ግን በዚህ መስመር ተቃኝቶ ሀገርን የማተራመስ አላማ ያነገበ ነበር ይላሉ፡፡
“መንግስት ምርጫን አስታኮ ነው እርምጃ የሚወስደው የሚለው ግን ምናልባት አጋጣሚ ሊሆን ይችላል እንጂ በምርጫ ጉዳይ ኢህአዴግ ራሱን በእጩነት አቅርቦ ይወዳደራል እንጂ ሚዲያን በማፈን ምርጫን ለማሸነፍ በምንም መልኩ አያስብም” ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጦች በአንድ ላይ የተዘጉት በ97 ምርጫ ማግስት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ባለፈው ዓመት መንግስት ከአምስት በማያንሱ መፅሄቶችና በአንድ ጋዜጣ ላይ የመሠረተውን ክስ ተከትሎ አብዛኞቹ አሳታሚዎችና ጋዜጠኞች ከአገር የተሰደዱ ሲሆን የሚዲያ ተቋማቱም መዘጋታቸው ይታወሳል፡፡

መንግስት ልማቱ ግጭትን ለማስወገድ ያለመ ነው ብሏል

የተለያዩ የአለም አገራትን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን፣ የአፍሪካ ልማት ባንክንና ለጋሽ ተቋማትን ጨምሮ 27 አባላትን የያዘው ዲቨሎፕመንት አሲስታንስ ግሩፕ የተባለ አለማቀፍ ቡድን፤ በደቡብ ኦሞ በመከናወን ላይ የሚገኙ ሰፋፊ የመንግስት የስኳር ፕሮጀክቶች በአካባቢው ግጭቶችን ሊቀሰቅሱ እንደሚችሉ ባለፈው ረቡዕ ማስጠንቀቁን ብሉምበርግ ዘገበ፡፡
የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም በበኩላቸው፤ በደቡብ ኦሞ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ግጭትን ለመከላከል ያለሙ እንደሆኑና በአካባቢው የሚኖሩ ማህበረሰቦችም የልማት ዕቅዶቹን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ ለማስቻል በስፋት መሰራቱን ከብሉምበርግ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን ከቻይና ልማት ባንክ ባገኘው ብድር በደቡብ ኦሞ አካባቢ ስድስት የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባትና በ150 ሺህ ሄክታር ላይ የሸንኮራ አገዳ ልማት ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ የሸንኮራ አገዳ ልማቱ የአካባቢውን ነባር ነዋሪዎች አኗኗር ሊያቃውስ ይችላል ተብሎ እንደሚሰጋ ቡድኑ ማስታወቁን ገልጧል፡፡
በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች በስኳር ፕሮጀክቶቹ ውስጥ ለመስራት ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አካባቢው መግባታቸውም፣ በአካባቢው የጎሳ ግጭቶችን ሊቀሰቅስ ይችላል ያለው ቡድኑ፤ ፕሮጀክቶቹ  በአካባቢው የሚከናወኑ የንብ ማነብ፣ የከብት እርባታ፣ የእርሻና የመሳሰሉ ስራዎች ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የስኳር ፕሮጀክቶቹ ተግባራዊ በሚደረጉበት የደቡብ ኦሞ አካባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደር ጎሳዎች፣ በፕሮጀክቶቹ ሳቢያ የግጦሽ መሬት እጥረት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል፤ ፕሮጀክቶቹ በጥድፊያ መከናወናቸውም በአካባቢው ግጭቶች የመከሰት ዕድላቸውን ከፍ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግና ጉዳዩ በአግባቡ ካልተያዘም በአካባቢው አለመረጋጋት ሊከሰት እንደሚችል ቡድኑ ስጋቱን መግለጹንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
መንግስት በአካባቢው የሚያከናውናቸውን የስኳር ፕሮጀክቶች በተመለከተ ግልጽነትን ማሳደግ፣ የማህበረሰቦችን ሃሳብ ማስተናገድና የፕሮጀክቶቹ ትግበራ ላይ የሚታየውን ጥድፊያ በመቀነስ የልማት ሽግግሩ ግጭትን በማያስከትል መንገድ እንዲከናወን ማድረግ ይገባዋል ብሏል ቡድኑ፡፡
የቡድኑ አመራሮች ባለፈው ነሃሴ ወር ያደረጉትን ጉብኝት ጨምሮ ባለፉት ሶስት አመታት በተደጋጋሚ ወደ ደቡብ ኦሞ በማቅናት፣ ከስኳር ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን በመከናወን ላይ የሚገኘውን የመንግስት የመልሶ ማስፈር ፕሮግራም ተጽዕኖ በተመለከተ ግምገማ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ዜና
  • ለሀገር መሪዎች ማረፊያ ይሆናል ተብሏል
  • ባለቤቱ ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ናቸው

    ንብረትነቱ የሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ የሆነው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለ 7 ኮከብ ሆቴል ግንባታ እየተገባደደ ሲሆን ከመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት በፊት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ እየተገነባ ያለው ያለው ባለ 7 ኮከቡ ሆቴል፤ በዓለማቀፍ ደረጃ በርካታ ሆቴሎችን በሚያስተዳድረው ዌስቲን ሆቴልና ሪዞርት ኩባንያ ይተዳደራል ተብሏል፡፡
በሚድሮክ ኩባንያ የኮንስትራክሽን ክፍል የሚገነባው ይህ ዓለማቀፍ ሆቴል መጀመሪያ ላይ  የ350 ሚሊዮን ዶላር (ወደ 7 ቢሊዮን ብር ገደማ) በጀት የተያዘለት ቢሆንም ወደ ማጠናቀቂያው ሲቃረብ ከተያዘለት በጀት የ20 በመቶ ተጨማሪ የግንባታ ወጪ እንዳስፈለገው ተገልጿል፡፡
ሆቴሉ ከሂልተን፣ ሸራተን አዲስና ራዲሰን ብሉ ሆቴሎች ቀጥሎ አራተኛው የሀገር መሪዎችንና ከፍተኛ ባለስልጣናትን የሚያስተናግድ ሆቴል ይሆናል ተብሏል፡፡
ሆቴሉን የሚያስተዳድረው “ዌስቲን ሆቴልና ሪዞርት” ዓለማቀፍ እውቅና ባለው ስታር ውድ ሆቴልና ሪዞርት በ1994 (እኤአ) የተመሰረተ ሲሆን በአሁን ወቅት በ37 ሀገሮች 192 ሆቴሎችን ያስተዳድራል፡፡ በጠቅላላው በ102 ሺህ ስኩዬር ሜትር ላይ ያረፈው ሆቴሉ፤ 27 የፕሬዚዳንቶችና 31 የሚኒስትሮች መኝታ ክፍሎችን ጨምሮ 610 የመኝታ ክፍሎች፣ 3500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚቻል የስብሰባ አዳራሽን፣ 8 መካከለኛ ደረጃ ያላቸው የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ማካተቱ ታውቋል፡፡ 2‚200 ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል የልዩ ግብዣ አዳራሽም አለው ተብሏል - ሆቴሉ፡፡
በተጨማሪም ተንደላቀቁ የመኝታ ክፍሎች፣ በፕሬዚዳንቶችና በከፍተኛ የቢዝነስ ሰዎች ምጣኔ የተዘጋጁ ባርና ሬስቶራንቶች፣ የመዋኛ ገንዳና ስፓ፣ ዘመናዊ ክለብ፣ የተለያዩ የግብዣ አዳራሾች፣ የቢዝነስ ተቋማት እና ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ፓርክ ይኖረዋል ተብሏል፡

Published in ዜና

በአንድ ሳምንት ውስጥ 14 እና 16 ወራት እስራት ተፈርዶባቸዋል
   በሽብርተኝነት የተከሰሱት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ፍ/ቤት በመድፈር ወንጀል በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ከትናንት በስቲያ የእስራት ቅጣት የተላለፈባቸው ሲሆን ዳኛው ቅጣቱን ሲናገሩ ለ3ኛ ጊዜ ቢያጨበጭቡም ፍ/ቤቱ “የዛሬውን አልፈዋለሁ” በማለት ሌላ ቅጣት ከማስተላለፍ ተቆጥቧል፡፡
ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት ላይ ያቀረቡት አቤቱታ በፍ/ቤቱ ተቀባይነት ማጣቱን ተከትሎ የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም “በጭብጨባ ችሎት ደፍራችኋል” በሚል መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም እያንዳንዳቸው በ7 ወር እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው ሲሆን ተከሳሾቹ በድጋሚ በማጨብጨባቸውና “ያልተገባ ንግግር ተናግረዋል” በሚል ፍ/ቤቱ ችሎት በመድፈር ጥፋተኛ ናቸው ሲል ውሳኔ ሰጥቶ ቅጣት ለመወሰን ለትናንት በስቲያ ቀጥሮ ነበር፡፡
ከትናንት በስቲያ የዋለው ችሎትም ተከሳሾቹ ከመጀመሪያው ስህተታቸው ሳይማሩ በድጋሚ ችሎት በመድፈራቸው ተጨማሪ የ7 ወር እና 9 ወር እስር ቅጣት ወስኖባቸዋል፡፡
በጭብጨባ ፍ/ቤቱን ደፍረሃል የተባሉት የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ም/ቤት ም/ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ እና የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ ተጨማሪ የ7 ወር እስር ሲፈረድባቸው፣ በጭብጨባና “አሻንጉሊት ችሎት ነው” በሚል ንግግር ፍ/ቤቱን ደፍረዋል የተባሉት አቶ አብርሃ ደስታ ደግሞ በተጨማሪ የ9 ወር እስራት እንዲቀጡ ፍ/ቤቱ ወስኗል፡፡ ችሎት በመድፈር ወንጀል በጠቅላላው በአንድ ሳምንት ውስጥ አቶ የሽዋስ እና  አቶ ዳንኤል በ14 ወር እስራት እንዲሁም አቶ አብርሃ የ16 ወራት እስር ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ ከትናንት በስቲያ የቅጣት ውሳኔ ሲነገራቸው በድጋሚ ያጨበጨቡ ቢሆንም ፍ/ቤቱ በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ለእናንተም ተገቢ አይደለም” የሚል ማሳሰቢያ በመስጠት የዛሬውን አልፈነዋል ብሏል፡፡
ማክሰኞ መጋቢት 1 ቀን ተከሳሾቹ ችሎት በመድፈር የመጀመሪው የ7 ወር ቅጣት ሲጣልባቸው ፍ/ቤት አለመድፈራቸውንና በወቅቱ የተናገሩት በመማረራቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ችሎቱ እውነተኛ ችሎት ባለመሆኑም ችሎት አለመድፈራቸውን ጠቁመው ድርጊቱን የፈፀሙት ፍትህ እናገኛለን ብለው ባለማመናቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤቱ አመራሮቹ በሚገኙበት በእነ ዘላለም ወርቅ አገኘው መዝገብ ስር የተካተቱ 10 ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመስማት ተሰይሞ የነበረ ቢሆንም ጠበቆች “አልተዘጋጀንም፤ አጭር ቀጠሮ ይሰጠን” በማለታቸው ለመጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ለፓርቲ አመራሮቹ የፍ/ቤት መድፈር ወንጀል ቅጣት መነሻ የሆነው በሚገኙበት ማረሚያ ቤት ህሳስ 12 ከ 13 ቀን 2007 ዓ.ም አጥቢያ ባልታወቁ ሰዎች በተደረገ የሌሊት ፍተሻ ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶች ተወስዶብናል ብለው ላቀረቡት አቤቱታ ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን ምላሽ ፍ/ቤቱ ከተከሳሾች አቤቱታ ጋር መርምሮ አቤቱታውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ነው፡፡   

Published in ዜና

“የአራዳ ጊዮርጊስ ደብር በገንዘብ ብክነት እና በመልካም አስተዳደር እጦት መቸገሩ ተገለጸ” በሚል ርዕስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም የወጣውን ዘገባ  “የተባለው ሁሉ ሀሰት ነው” ሲሉ የደብሩ ማህበረ ካህናት አወገዙ፡፡
ዘገባው ከሃቅ የራቀ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለፁት ካህናቱ፤ በአስተዳዳሪውና በሰራተኛው መካከል ችግር አለ ተብሎ በዘገባው የተጠቀሰው ከእውነት  የራቀ ነው ብለዋል፡፡ “የደብሩ አስተዳዳሪ ሰራተኞችና ባለሙያዎችን በዛቻ ቃል ያሸማቅቃሉ የተባለውም ፈፅሞ ሃሰት ነው፤ አባታችን ይኸን አያደርጉም” ሲሉ  ተናግረዋል፡፡
“በአሁን ሰዓት ያለው አስተዳደር፣ ሰበካ ጉባኤውና የልማት ኮሚቴው በልዩ ሁኔታ ያለምንም ተፅዕኖ ሁሉም በራሱ በጎ ፍቃድ እየሰራ ነው” ብለዋል፤ ካህናቱን ወክለው የተናገሩት ሊቀ ካህናት ቄሰ ገበዝ ብርሃኑ፡፡
መምህር ወልደሰላም አለሙ በበኩላቸው፤ ደብሩ የሰላም፣ የአንድነትና የልማት ቦታ መሆኑን ጠቅሰው “በመልክአ መንክራት ኃይሉ አብርሃ የሚመራው አስተዳደር የሰላም አስተዳደር ነው” ብለዋል፡፡ በዘገባው ላይ ለግንባታ የተያዘው በጀት ከ61 ቢሊዮን ብር ወደ 80 ሚሊዮን ብር አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት እንዲያድግ ተደርጓል የተባለው ውል ተደርጎ ሁላችንም አምነንበትና ፈርመን እድሳት የተደረገበት ነው እንጂ የደብሩ አስተዳዳሪ ብቻቸውን የወሰኑት ነገር የለም ብለዋል፡፡የደብሩ አስተዳዳሪ ለማህበረ ካህናቱ ሳያሳውቁ በራሳቸው የወሰኑት ውሳኔም የለም ሲሉም የአዲስ አድማስ ዘገባን አስተባብለዋል፡፡ “በኮንተራክተር መረጣ ወቅትም አስተዳዳሪው አማክረውን ነው ኮንትራክተሩ እንዲመረጥ የተደረገው” ብለዋል፤ መምህር ወልደ ሰላም፡፡
አስተዳዳሪው እንኳን ሰራተኛን ሊያሸማቅቁ የተጣላን አስታራቂና ሃገሪቷ ሰላም የምትሆነው ቤተክርስቲያን ሰላም ስትሆን ነው ብለው የሚያምኑ አለቃችን ናቸው ብለዋል - መምህር ወልደሰላም፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ የገንዘብ ብክነት እንዳለ ተደርጎ የተዘገበው ሃሰት ነው ያሉት መምህሩ፤ እንኳን በገንዘብ ብክነት ሊታማ ከ40 ሚሊዮን በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ያለው ነው ብለዋል፡፡ ይህም ለአዲስ አበባ አድባራት በሙሉ ምሳሌ እንደሆነ በመግለፅ፡፡
የማህበረ ካህናቱ ተወካዮች “አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከቤተክርስቲያናችን ላይ እጁን ያንሳ” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡  


Published in ዜና
Page 11 of 21