Monday, 09 March 2015 11:50

ሴቶች በዋሉበት

ማስታወሻነቱ
ለድምጻዊት ንግሥት አበበ

    እንደ እምነታችን እና እንደ ባህላችን ሁሉ ቋንቋችንም ለወንድ ያዳላል፡፡ ወንድ የሚለው ቃል ቃጭል ማንጠልጠልን ብቻ የሚገልጽ ቃል አይደለም፡፡ በተለመደው አማርኛ፣አንድ ሰው ወንድ ነው ሲባል ጀግና ነው ልበ ሙሉ ነው፤ ማለት ነው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ወደ ጦር ሜዳ ለመዝመት የተዘጋጀ ካህን፤
ወግጅልኝ ዜማ ወግጅልኝ ቅኔ
ወንዶች በዋሉበት መዋሌ ነው እኔ
…ብሎ ተቀኝቷል፡፡ በቅኔው ውስጥ ወንዶች ሲል ጀግኖች ማለቱ ነው፡፡ ወንድ የሚለው ቃል ጀግና ለሚለው አቻ ከሆነ፣ በተቃራኒው ሴት ማለት ፈሪ ማለት እንደሆነ መገመት አያቅትም፡፡ አንዲት ሞት የምትንቅ ሴት በጉልህ ብቅ ካለች ወንድ ናት ትባላለች፡፡ ከሴት ባህርይዋ አፈንግጣለች ማለት ነው፡፡ ይህ ትልቅ ፍርደ-ገምድልነት መሆኑን ለመረዳት የሚፈልግ ታሪክን ወደ ኋላ ዞር ብሎ ይመልከት፡፡ ወንዶች ለብቻቸው የተሳተፉበት ጦር ሜዳ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡ ሴቶች ባዋላጅነት ከነበራቸው የማይተናነስ ሚና በጦር ሜዳ ተጫውተዋል። እናቶቻችን በጦር ወቅት፣መሳርያ ያቀርቡ ነበር፡፡ ምግብ ያቀርቡ ነበር፡፡ ሀሳብ ያቀርቡ ነበር፡፡ ልብ ያቀርቡ ነበር፡፡ ደስታ ያቀርቡ ነበር፡፡ ኧረ ምኑ ቅጡ
መሣርያ
ዘመናዊ ጠመንጃ ከመምጣቱ በፊት ሴቶች፣ ከሰልና ጨው ወቅጠው፣ባሩድ ያሰናዱ እንደነበር ያውቃሉ? ባሩዱ ዳሄራ ይባላል፡፡
ሴቶች ተሰብሰቡ እንውቀጥ ዳሄራ
ክርክር አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ
እንዲሉ እናቶች፡፡ የመጀመርያው የጦር መሳርያ ፋብሪካ የእናቶቻችን ሙቀጫ መሆኑን ልብ እንበል፡፡
በነገራችን ላይ ይሄን ግጥም ሴቶች የዘፈኑት፣ንጉስ ምኒልክ ራስ አዳል ጋ ጦርነት ሊያደርጉ ሲሰናዱ ነው። ግጥሙ የዋዛ ግጥም አይደለም፡፡ የወቅቱን የፖለቲካ መስመር በስንኝ የሚተነብይ ነው፡፡እንግዲህ ሴቶች ባንድ በሙቀጫ ዙርያ፣ ማህበረሰቡን፡- ኬሚስት፣ገጣሚና የፖለቲካ ተንታኝ ሆነው ማገልገላቸውን ልብ እንበል፡፡
ምግብ
ድሮ ወታደር እንደ እንደ ቅርብ ጊዜው ኮቸሮውን በላስቲኩ፣ ውሀውን በኮዳ ይዞ የሚዘምት አልነበረም፡፡ ምግቡና መጠጡን እዚያው ከጦር ሜዳ ነው የሚያገኘው። በዚህ የተነሣ ሴቶች፣ማጀታቸውን ወደ ጦር ሜዳ ይዘውት መዝመት ነበረባቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ስለ ጦር ሜዳ ስናስብ ቶሎ የሚመጣልን ፉከራ፣ ሽለላ፣ ሁልጊዜ የሚያባርር አርበኛ፣ ሁልጊዜ የሚወድቅ ጠላት፤የመድፍ ተኩስ፣ የባሩድ ሽታ ወዘተ ነው፡፡ በጦር ሜዳ እንጀራ ሲጋገር፣ ወጥ ሲሰራ፣ ጠጅ ሲጣል ማሰብ ለአእምሮ የተለመደ አይደለም፡፡ ግና ከባሩድ ጭስ በማይተናነስ መጠን የማእድ ቤት ጭስ ታሪክ ሰርቷል፡፡
ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረስላሴ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹እንዲህም እየሆነ፣ አጤ ምኒልክ ባዳራሹ እቴጌ ጣይቱ በልፍኝ ባለሟሎችዎን ወይዛዝሩን ይዘው ግብሩ አንድ ቀን ሳይጎድል፣ ይዘምታሉ፡፡ ከዘመቻ ላይ ጠጁ ማሩ አለመጉደሉ፣ስለምንድነው ያልህ እንደሆነ ይህነን ታሪክ መመልከት ነው፡፡ በስድስት ድንኩዋን እንጀራው ሲጋገር ሲያድር፣ በአራት ደንኳን ወጡ ሲሠራ ሲያድር፣ ጠጁ በቀንድ በኮዳ ደግሞ ሶስት መቶ ስድስት መቶ የሚሆን ገንቦኛ ሲጓዝ ግብሩ ይጎድል ይመስልሀል››
በኔ ግምት፣ ጸሐፌ  ትእዛዙ ገብረስላሴን ያክል ለሴቶችና ሰሴትኛ አስተያየት ቦታ የሰጠ ጥንታዊ ታሪክ ጸሐፊ ያለ አይመስለኝም፡፡ ባብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ያዳራሽና ያደባባይ ታሪክ ነው፡፡ የእልፍኝ (ጓዳ )ታሪክ ከቁጥር አይገባም፡፡ ገብረ ስላሴ ግን፣ ጦር ሜዳ ዘምተው፣ መድፉን፣ነፍጡን እንደሚቆጥሩ ሁሉ እልፍኝ ገብተው ምጣዱን እንጀራውን ቆጥረውልናል፡፡ አንዳንዴ በማጀቱና በጦር ሜዳው መካከል ያለውን ድንበር በዘይቤ ያፈርሱታል፡፡ ለምሳሌ፣የኢትዮጵያ አርበኞችን የስነ ልቦና ዝግጅት ሲገልጹ፤ ‹‹የሠራዊቱ ልብ እንደ ምጣድ ግሞ ነበር›› ይላሉ፡፡ የሰራዊቱን ወኔ ለመግለጽ የተመረጠው የጋለ ብረት አይደለም፡፡ እሳተ ገሞራ አይደለም፡፡ ወንድ ያስተውለዋል ተብሎ የማይታሰበው ‹‹የጋለ ምጣድ ነው›› (ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ፤ ገጽ 241)
የሆነው ሆኖ፣ ሴቶቹ ‹‹ግብሩ አንድ ቀን ሳይጎድል›› ያን ያህል ጊዜ፣ (ከጥቅምት እስከ የካቲት)ያን የሚያክል መንገድ (ከእንጦጦ፣ አድዋ) ሰራዊቱን መመገብ መቻል ከባድ መስዋእትነት ነው፡፡ ለዚህ መስዋእትነት ክብር ባንሰጥ የእናቶቻችን አጽም ወስፌ ሆኖ ይወጋናል፡
ሃሳብ
የብልህ ሴቶች መላ ታሪክ ቀይሯል፡፡ ዝነኛው ምሳሌ እቴጌ ጣይቱ በመቀሌ ጦርነት ያቀረቡት የጦር ስልት ነው፡፡ እቴጌ ከተለመደው የወንዶች ደካማ ጎን ከሆነውና ወገንን ለዘግናኝ እልቂት ከሚዳርገው እሳት-ራታዊ የውግያ ልማድ ወጣ ብለው ማሰብ በጣልያኖች አይበገሬ ምሽግ አቅራቢያ ያለው ኩሬ በቁጥጥር ስር እንዲውል አዘዙ፡፡ መቀሌ ላይ ጣልያኖች የተደፈሩት እንደ ንግስተ ሳባ በውሃ ጥም ምክንያት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሴቶች ጦር ሜዳ ላይ መሳርያ ያቀርቡ ነበር፡፡ ምግብ ያቀርቡ ነበር፡፡ ሌላ ምን ቀረ? የሚቀረው ልብ ማቅረብ ነው፡፡ በጦርነት ውስጥ ሴቶች ለጅግኖች ልብ ያቀርቡ ነበር ብል አሁንስ  አበዛኸው የሚለኝ ይኖር ይሆናል፡፡ ሽንገላ አይደለም ሐቅ ነው፡፡
ዘመናዊ አዋጊ መኮንን ጠላቶቹን ወደፊት እንዲሄዱለት ሲፈልግ፣ ከኋላ እየተከተለ ባቀባበለው ሽጉጥ እያስፈራራ ይገፋቸዋል፡፡ ሲሸሽ የተገኘ ወታደር የሞት ፍርድ የሚፈረድበት አጋጣሚም ነበር፡፡ በወገን ጥይት ከመሞት በጠላት ጥይት ከመሞት የቱ ይሻልሀል ነው ምርጫው፡፡የጥንቶቹ የጦር ሰዎች ግን ሌላ መንገድ ነበራቸው፡፡ ከፍርሀት  ይልቅ እፍረት የሚባለውን ስሜት ጀግና ለመፍጠርያ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ለዚህ ቀላሉ መንገድ ሴቶች ከወንዶች ጀርባ እንዲሰለፉ ማድረግ ነው፡፡ ወንዶች ተዋጊ ከሆኑ የውጊያው ደረጃ መዳቢዎች ሴቶች ናቸው፡፡ በሚስቱ ወይም በውሽማው እየታየ መሆኑ ሲገባው የቆጠባትን ጉልበት ያወጣታል፡፡ ከለገመ ይበረታል፡፡
ዋልተር ፕላውደን የተባለ በዘመነ መሳፍነት ዘመን አገራችንን የጎበኘ ፈረንጅ እንደ መዘገበልን፤ የወሎ ኦሮሞ ሴቶች ጦር ሜዳ ላይ ከወገን ጦር ጀርባ ይሆኑና፣ ወኔ የሚያነሳሱ ዘፈኖችን ይዘፍናሉ፡፡ የጀግንነት ቅኔዎች ይቀኛሉ፡፡ የሚሸሽ ወታደር ሲያዩ ፊቱን ወደ ጠላቶቹ እንዲያዞር ይገስጻሉ፡፡ ፕላውደን የተመለከታቸው ሴቶች ኣረሆ ይባላሉ፡፡ ኣረሆ የሚለው ስም አዳራሽ፣ መድረክ ላይ ሳይሆን አረህ ላይ ቆመው ስለሚዘፍኑ የተሰጣቸው ስያሜ ነው፡፡
ይህ በወሎ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡
አለቃ ተክለ ኢየሱስ ከደርቡሽ ጋር በተደረገው ጦርነት፣ የጎጃም ጦር ከተሸነፈና ሽሽት ከጀመረ በኋላ የተከሰተ አንድ ትእይንት ሲተርኩ፡-
‹‹ያን ቀን ላቀች የምትባል፣ ወረሴክ ጦር አጋጣሚ ስትሸሽ በቅሎዋ ጥሏት ከመንገድ ወደቀች፡፡ያን ጊዜ የንጉሱ ጀግና ተገኝ አባ ጆፌ የሚባል ደርቡሽን ሲፈጅ ውሎ፣ ሦስት ስናድር ማርኮ ግራ ቀኝ አንግቶ በጠገበ ፈረስ ደረሰላት፡፡ እርሷም እንዲህ አለች፡-
እኔስ ደከመኝ ተፋሁ አሞት
አዙር ተገኝ በንጉሱ ሞት
…ብላ አቅራራች፡፡ የዚህን ጊዜ ተገኝ አባ ጆፌ ከወደቀችበት ክንዷን ነጥቆ ከፈረሱ ላይ አስፈንጥሮ ታደጋት፡፡ ከደርቡሽ ጋ እየዞረ እየተታኮሰ ስንኳን ርሷን ሌላውን ደካማ እያበረታታ አወጣው›› ሲሉ ተርከውልናል፡፡
ጀግናው ሰው የወይዘሮ ላቀችን እንጉርጉሮ እስኪሰማ ድረስ በሽሽት ላይ ነበር፡፡ ለዝያውም ሦስት የተማረከ ስናድር አነግቶ፡፡ የሴትዮዋ እንጉርጉሮ ተአምር መፍጠሩን ልብ እንበል፡፡ “አዙር ተገኝ” ስትለው፣ የፈረሱን አቅጣጫ አዞረ፡፡ ማፈግፈጉ ቀርቶ ማጥቃት ጀመረ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አሳዳጅ የነበረው መልአከ ሞት አሁን ተሳዳጅ ሆነ፡፡ ምናልባት ከጳጳስ ግዝት በላይ፣ ከአዋጊ ማስፈራሪያ በላይ ከሴት አንደበት የሚወጣ ‹‹አዙር›› የሚል ቃል ኃይል ነበረው፡፡ ሴቶች ጀግናው ልብ ሲከዳው ልብ ሲያቀርቡ እንደኖሩ ታሪክ ጮክ ብሎ እንዲህ ይመሰክራል፡-
በአድዋ የሆነውም እንዲህ ነው፡፡
እቴጌ ጣይቱ ባድዋ ከሴት ሰራዊታቸው ጋራ ሆነው ጥቁር ጃንጥላ አስይዘው፣ በባዶ እግራቸው አየተራመዱ ከሰራዊቱ ኋላ ይከተላሉ፡፡ የሆነ ጊዜ ላይ ሰራዊቱ የጠላት ጦር ተጭኖት እንደ መሸሽ ሲል እቴጌ፤
‹አይዞህ አንተ… ምን ሆነሀል! ድሉ የእኛ ነው በለው› አሉት፡፡ ሰውም የተናገሩትን ቃልና እቴጌን ባየ ጊዜ ሴት ሲያጣና ወንድ መሸሽ አይሆንለትምና ጸጥ አለ››
ወኔ እንደ እጃችን እንደ እግራችን በተፈጥሮ ይዘነው የምንወለደው አይደለም፡፡ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ እንጂ ከነጀግንነቱ ዱብ አይልም፡፡ ጀግንነት የማህበራዊ ግንኙነት ውጤት ነው፡፡
ሴቶች በጦርነት ውስጥ የተለመደውን ስጋዊ ደስታ በመስጠትም ያገለግሉ ነበር፡፡
ሩካቤና ትግል አብረው አይሄዱም የሚለው የቅርብ ፍልስፍና ነው፡፡ የህወሐትን የትግል ታሪክ የሚጽፉ ፀሐፊዎች እንደሚነግሩን፤ በትግል የመጀመርያ አመታት ወሲብ ለትልቅ ጉዳት የሚዳርግ ወንጀል ነበር፡፡ ይህ ከተፈጥሮ ውጭ ከትውፊት ውጭ የሆነ ነገር አባቶቻችን አይጋሩትም፡፡ ቀደምቶቻችን በዚህ ጉዳይ ላይ ሆደ-ሰፊ ናቸው፡፡ ወታደር ‹‹አብሬሽ አድሬ ሲነጋ ልሙት›› ይል ይመስል፣ በጦር ዋዜማ ካብሮ ዘማች ሚስቱ ጋር ያድራል። የቅርቦቹ ወሲብ የከለከሉት ጉልበት ያዳክማል፤ ትኩረት ይሰርቃል ብለው ሊሆን ይችላል፡፡ ለጥንቶቹ ግን ትኩረት የሚሰርቀው ማድረግ ሳይሆን መናፈቅ ነው፡፡ ምኒልክ የሚታወቁበት አንዱ ጥቅስ‹‹ አመልህን በጉያህ ስንቅህን ባህያህ›› የሚል መሆኑን አንርሳ፡፡ ሌሎችን እስካልረበሸ ድረስ፣ የግል ጉዳይህ ከዘመቻ አይከለክልህም የሚል ሐሳብ የያዘ ነው፡፡
የወገን ጦር ቀንቶት ድል ከነሣ ሴቶች ሰለባ ይሰበስባሉ፤ ድል  ከተነሣ ራሳቸው ሰለባ ሆነው ይሰበሰባሉ፡፡ በባርነት ይፈነገላሉ፡፡ ውበታቸው የድል አድራጊውን አይን የሚስብ  ከሆነ የጭን ገረድ፣ ጉልበታቸው የድል ነሺውን አይን የሚማርክ ከሆነ ባርያ ይሆናሉ፡፡ ለድል አደራጊ ጀርባ ላሉ ሴቶች ‹‹እንኳን እናቱ የወለደችው፣ አማቱ ኮራች የተጋባችው›› እየተባለ የተዘፈነውን ያክል በለስ ላልቀናቸው፣ ቀን ለጎደለባቸው ምርኮኛ ሴቶች እንጉርጉሮ ሲወርድ ኖሯል፡፡ ባሰበኩት ቁጥር ሆዴን የሚያላውሰው፣ የገላውዲዮስ ዜና መዋእል ያንጎራጎረውን ላካፍል፡፡
ወለተ ኢትዮጵያ ስትትከደን፣ አእዳ ለዘማ እሰወአነዳ
ወትለብስ ሰቀከመሰሌዳ
ወትዕንቅጋ ጋህየንተሐብለተወርቅዘውስተክሳዳ
ወህየንተ ቤተ-ወይን ወማህሌት ጽጌ እለይ ላሕውትረሲ ዓውዳ
ዐውደባለዲበርእሳህየንተመዓዛዕፍረትወማየሬዳ
ትርጉሙ
የኢትዮጵያ ልጅ ቁርበት ደርባ
እንደ ሰሌዳ ማቅ ተከናንባ
በወርቅ ድሪሐ ብል ፋንታ አንገቷ ቀንበር ጠልቆላት
የዘፈን ቤቷ ፈርሶ
አደባባይዋ በልቅሶ
የትካዜ ጭጋግ ለብሶ
በሽቶ ማእዛና በጽጌረዳ ፈሳሽ ፋንታ
በገጽዋ ትቢያ ተነስንሶ፡፡
ጦር ካለምርኮ ብቻ ሳይሆን ሞት አለ፡፡ ሞት ካለ አልቃሽ ሴቶች ይኖራሉ፡፡ የሴቶች የቀብር ላይ እንጉርጉሮ የወጣለት ፍልስፍና ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፍልስፍና የተወለደው ከእናቶቻችን ዝቅዝቅ ነጠላ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ስለ ጥፋት፣ ስለ ሞት፣ ስለ ሕይወት፣ ስለ እምነት የነበራቸውን አስተያየት የምናየው ሙሾአቸው ውስጥ ነው፡፡ የልቅሶ ግጥሞች ስሜት- መራሽ ስለሆኑ እንደ ሽንት ቤት ግድግዳ ጽሁፍ እውነተኛውን የልብ ጩኸት የሚገልጹ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜም ከዘልማዱ አመለካከት ጋር የሚጋጩ ሀሳቦች የሚያመነጩት አልቃሽ ሴቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከቴዎድሮስ ጋር በተደረገ ጦርነት የባእታ ማርያም ቤተክርስትያን ቃጠሎን የተመለከተች አንድ አልቃሽ የሚከተለውን አመጻ ያዘለ እንጉርጉሮ አንጎራጉራ ነበር፡፡
ሰማይ ላይ ሆነህ ስታላግጥ በሰው
እናትህ ነደደች ሐዘኑን ቅመሰው
አሳቡ በጣም አስቂኝ በዛው ልክ በጣም አደገኛ ነው። ፈጣሪን ቅዱስ፣ ለፍጥረቱ አዛኝ አድርጎ በሚያምን ማህበረሰብ ውስጥ እግዜርን እንደ አለቃ ገብረሀና በሰው ውድቀት የሚስቅ አድርጋ ማቅረቧ የድፍረቷን ልክ የሚመሰክር ነው፡፡ ሴትዮዋ ‹‹እግዜያብሄር ሰጠ፣እግዚአብሄር ነሣ›› እያለ የመጣውን ሁሉ በጅልነትም በለው በጸጋ ተሸክሞ ከሚኖረው አብዛኛው ሰው የተለየች ናት፡፡
ሐሳቧ ከዘልማዱ አመለካከት ጋር መጋጨቱን የምንረዳው የሚከተለውን አጸፋ ምላሽ ማስከተሉን ስናነብ ነው፡፡ ለተለመደው ሐሳብ ወኪል ሆነው አጸፋውን  ያቀረቡት ኅሩይ ወልደስላሴ፣ የተባሉት ባለስልጣን ጸሐፊ ናቸው፡፡ የልቅሶ ዜማ በሚለው መጽሀፋቸው ይህንን ግጥም ከጠቀሱ በኋላ፤
‹‹ይህች ሴት (ገጣሚዋን ማለታቸው ነው) ባለእውቀት በብስጭትና በሀዘን እንዲህ ብላ ገጠመች እንጂ እግዚአብሔርስ የሰው እጅ ከሰራው ከቤተክርስትያን ይልቅ እርሱ በሠራው በሠው መቃጠል እንዲያዝን የታወቀ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡፡›› ይሉና የቅዱስ ጳውሎስን ጥቅስ ያስከትላሉ፡፡
በማመንና በማመዛዘን መካከል ያለ ግብግብ በግልጥ ይታያል፡፡ ለኅሩይ የእውቀት ምንጭ የተለመደው መጽሐፍ ነው፡፡ ሴትዮዋ ግን በራሷ ልብ ውስጥ የፈለቀውን እውቀት  አዳምጣለች፡፡ ኅሩይ፣ የጳውሎስን ልብ ማዳመጥ በቂ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ የጳውሎስ ድምጽ የተረጋገጠ እውቀት ምንጭ ሆኖላቸዋል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ አናጋሪነት ሳይሆን ‹‹በብስጭትና በሐዘን›› ገፋፊነት የቀረበ በመሆኑ አልተቀበሉትም፡፡
ይህ በሰማያዊ ሀይል የሚያምን ሰው፣ በምድር ውስጥ የሚከሰቱ ግራ የሚያጋቡ ነገሮችን የሚመለከት ጤነኛ ሰው፣ ከእለታት አንድ ቀን እንደ አልቃሿ ሴትዮ ‹‹በሰማይ ላይ ሆነህ ስታላግጥ በሰው›› ማለቱ አይቀርም፡፡

Published in ህብረተሰብ
Monday, 09 March 2015 11:46

ለመሆኑ ሳቅ የማን ናት?

የእግዚአብሔር ወይንስ የሰይጣን?.... ሰይጣን ምን አባቱ ቆርጦት ይስቃል! ስራውን ሰርቶ ሲጨርስ የት ተወስዶ እንደሚጣል እያወቀ ይቆዝም እንጂ ምን ያስቀዋል!...
ሳቅማ የሰው ልጅ ብቸኛ አንጡራ ሀብቱ ናት። ፍርሐቱን የሚያሸንፍባት….ከአቅሙ በላይ ውድ አድርገው የሸጡለትን ህይወቱን ቀለል፣ ረከስ የሚያደርግባት እፎይታው፡፡ ሳቅማ የእኔ ናት፡፡ ግን ታዲያ ለምንድነው ስቄ የማላውቀው?
መሳቅ ስላለብኝ የማሳቂያ ምክንያት መፍጠር አስፈልጐኛል፡፡ ግን እኮ ሳቅ ምክንያት አያሻውም፡፡ የአመለካከት መንገድን መቀየር ብቻ ነው ዋናው ነገር። ትንሽ መጃጃል ማለቴ ነው፡፡ ጨካኝ መሆን ሳይሆን መጃጃል፡፡
“በማን ላይ ነው የምትስቀው…..ምን ያስቅሀል?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ቢሆንም፤ ምክንያት መፍጠር አያስፈልገኝም፡፡ በሁላችሁም ላይ እና በሁሉም ነገር ነው የምስቀው፡፡ የሳቅ ት/ቤቱ ራሱ ያስቀኛል፡፡ ስለ ሳቅ የምፅፈው ራሱ እየሳቅሁ አለመሆኔ በውስጤ ያስቀኛል፡፡ “እያረሩ ማሳቅም” የሳቅ አይነት ነው…ኮርሱ በሳቅ ት/ቤታችን ስለመስጠቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
እንደ ሃይማኖት ተቋሞች ሳቅን በድብቅ የሚያወግዝ ያለ አይመስለኝም፡፡ ፈጣሪን መፍራት ዋነኛው መርህ በሆነበት ስፍራ ሳቅ ሊፈቀድ አይችልም፡፡ ቀጥ ባለ በአናቱ ብቻ የሚታወቅ ነገርን ዘቅዝቆ በማየት ድፍረት ነው ሳቅ የሚፈጠረው፡፡ ጠንካራ እምነትን ወደ ጥርጣሬ በሚለውጥ እይታ ውስጥ እንቆቅልሽ ይወለዳል፡፡ መገልፈጥ ሳቅ አይደለም…ከጥርስ መደርደር ባሻገር…  ሀሳብም ሲደመርበት ቀልድም ሳቅ ይሆናል፡፡
ሳቅ መገልፈጥ አይደለም፡፡ ጥሩ ሃሳብ ያስፈልገዋል። ለጥሩ ሃሳብ ደግሞ ጥሩ እውቀት አስቀድሞ መኖር አለበት፡፡ ሃሳብ እና እውቀት ኖሮት የነፃነት ፍርሃት ያለበት ሳቅን ከቀልድ ውስጥ ሊያመነጭ አይችልም፡፡ … ምናልባት የኔም የሳቅ ድርቀት ከእዚህ ጉድለቶች በአንዱ ምክኒያት ይሆናል፡፡
ለመንፈሳዊያኑ ሳቅ የስጋ ሀጢአት ተደርጐ በግልፅም ባይሆን መወሰዱ አይቀርም፡፡ ሳቅን ከተሳቀበት ምክንያት ነጥሎ ማየት አይቻልምና፡፡ በሙዝ ልጣጭ ተንሸራትቶ የወደቀው ሰው ላይ መሳቅ…መስቀል ተሸክሞ ከወደቀው መሲህ ላይ ከመሳቅ ጋር ረቂቅ የሆነ ትስስር አለው፡፡ የፈረንሳይ የካርቱን መጽሔት አዘጋጆች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉትም በዚሁ የሳቅ ግንኙነት ነው፡፡
ሳቅ የሰው ልጅ የግል ንብረቱ ናት፡፡ የማህበረሰብ አይደለችም፡፡ ማህበረሰብ ተግባብቶ በሳቀው ቀልድ ሌላ የሚያስኮርፈው አካል ከበስተጀርባ አለው፡፡ ሳቅ ብቻውን አይደለም፡፡ የተሳቀበት ነገር እና ምክኒያቱ አብሮት አለ፡፡ የሳቀው ከተሳቀበት እኩል ደስተኛ እንዲሆን አይጠበቅም። ሳቅ የነፃነት መገለጫ ነው፤ ግን የአንዱ ነፃነት ሌላውን በማብሸቅ አርነቱን የሚቀዳጅ ነው፡፡ መንግስት በቀለደው ቀልድ ህዝብ አይስቅም፡፡ ይገለፍጥ እንደሆን እንጂ…
ስለዚህ ሳቅ የግለሰብ ናት፡፡ “On the road” የተባለ የጃክ ኬሩዋክ ድርሰት ላይ አንድ ገፀ ባህርይ አለ፡፡ ምግብ እየተመገበ ተጎልቶ ከነበረበት መአድ ምን አይነት ቀልድ በጭንቅላቱ እንደተፈጠረ ባይታወቅም…ከጠረጴዛው ተነስቶ መሳቅ ጀምሮ…እየተንደፋደፈ እስከ ከተማዋ ጠረፍ ድረስ ቀኑን ሙሉ ሲስቅ ዋለ፡፡ የዚህ ኔግሮ ሰውዬ ሳቅ በአይነቱ ለየት የሚልብኝ የሳቁ ምክንያት በደራሲው ባለመገለፁ ነው፡፡ ሳቅ የግለሰብ ንብረት መሆኗንም ለእኔ ያረጋግጥልኛል፡፡ ከራስ ጋር ብቻ የሚሳቅ ሳቅ… ለሳቂው ለራሱ ቅኔ ነው፤ ለተመልካች ግን እብደት፡፡
“ምን አሳቀህ?” ተብሎ ጥያቄ ከቀረበ በኋላ የሳቁ ባለቤት ዕይታ እና ሳቁን ለመዋስ እየሞከረ ያለው ሰው እየታ ካልተጣጣሙ…ቅራኔ ሊከሰት ይችላል፡፡ ወይ የሳቅ ነፃነት ጉልበቱ ይደክማል፡፡ የሳቅ ሙሉ ነፃነት ግለሰብ አእምሮ ውስጥ ያለ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወጥቶ ለሌላ ለማቀበል ማለዘብ እና መደራደር ይገደዳል፡፡
ሁሉም ቀልድ ከፍ ተደርጐ የሚታይ ነገርን ዝቅ በማድረግ የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡ እስታሊን፣ ሌኒን እና ትሮትስኪ “Animal farm” ላይ ያሉትን አሳሞች ይሆናሉ። ሰራተኛው መደብ ፈረስ ተደርጐ ይመሰላል። ከፍታው ላይ ክብራቸውን ያደላደሉት እንጂ ሲወድቁ የሚያስቁት ውዳቂውማ ድሮውኑ ትራጀዲ ነው፡፡ … ድሮውኑ ጉድጓድ ውስጥ ባሉት ለመሳቅ ያስቸግራል፡፡
ከፍታው ላይ በነበረበት ሰዓት ይፈራ የነበረው ነገር በሳቅ ዝቅ ብሎ ትንሽ እንዲረክስ፣ የደረበው ጭንብልም ተቀዶ እንዲወድቅ ይሆናል፡፡ በዚህ የሳቅ ሂደት ከፍታው ላይ ለነበረው ነገር፣ ሰው፣ አምላክ ከቀልዱ በፊት የነበረው ፍርሐት ከሳቁ በኋላ አይኖርም፤ ወይንም ዋጋው ይረክሳል። ሳቅ ተነግሮት መሳቅ ባይፈልግ እንኳን አምልጦት የሳቀ፣ ለሳቀበት ነገር ከዚህ በፊት ይሰማው የነበረውን ፍርሐት…ክብር በመጠኑም ቢሆን አጥቷል፡፡
ስለዚህም፤ ክብር እንዲረክስ በማይፈለግበት ስፍራ ቀልድ አይፈቀድም፡፡ ከቀልድ ወይንም ገላጭ እንቆቅልሽ ፍቺ ውጭ የሚወጣ ሳቅ ደግሞ ለአእምሮ ችግረኞች እና ቂሎች የተመደበ በመሆኑ … ቦታ አይሰጠውም፡፡
ሳቅ የነፃ ግለሰቦች እና የቂሎች ናት፡፡ ምናልባትም ነፃ ግለሰቦች ቂሎች ብቻ ናቸው፡፡
ሁሉም እውነተኛ ሳቅ ውስጥ ከዚህ በፊት ተገልጦ የማያውቅ እውነት አለ፡፡ እውነቱ ግን የሳቁ ምክኒያት የሆነው ነገር ከዚህ በፊት ይታይ የነበረበትን መንገድ አደብዝዞ የሚፈካ በመሆኑ በሳቅ ውስጥ አዲስ ገፅታ ይዞ እውነቱ ሲወለድ የድሮውን ገፅታ ግን ይገድለዋል። የድሮው ገፅታው እንዲሞት የማይሹ በሳቅ እንዲረክስ አይፈቅዱም፡፡ በቀልድ መወጋት በጦር ከመወጋት የበለጠ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ የተወጋው ነገር እንዳለበት (አለሁ እንዳለበት) ከፍታ የአወዳደቁ ርቀት እና ህመሙ ይወሰናል፡፡
አንድ ህፃን ሊስትሮ በጥፊ ሲመታ ብዙ ሰው ሊስቅ ይችላል፡፡ አንድ ሽማግሌ ግን በጥፊ ቢመታ ቀልድ አይሆንም፡፡ ቀልድ እንዲሆን የማህበረሰብ ውሉ አይፈቅድለትም፡፡ የግለሰብ የውስጥ ግዛት ግን ብቻዋን ትስቃለች፡፡ ከፍ ካለበት ቦታ በሳቅ የወረደው ሁሉ ለግለሰቡን ፍርሐት በሆነ ነፃነት ተክቶ ነውና፡፡
ብዙ ፍርሃት እና መፈራራት በነገሰበት መንፈስ ውስጥ ለግለሰብ ከሳቅ የበለጠ ወጌሻ የለም፡፡ ሳቅ ከጥበባቱ መደርደሪያ ወጥታ (ወይ) ፋርማሲ መደብር መደርደሪያ ላይ መቀመጥ ሳይኖርባት አይቀርም፡፡ ፍርሐት እና መጠባበቅን ዋጋቸውን ረከስ አድርጋ… ቀልዳባቸው ትንሽ ነፃነት እና የእፎይታ የተናፈሰ አየር እንዲገባ መፍቀድ ትችላለች፡፡
ክርስቶስ ፍቅርን ሰበከ…ሞት እና መንግስት ደግሞ ፍርሐትን ሰበኩን፡፡ ሳቅ ምናልባት የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ፍርሐትን የሚያበዛ ጭንቅላት እና ትካዜን አጥብቀን እንድንይዝ የሚያደርግ ማንኛውም ተቋም ላይ በጥቂቱም ቢሆን መሳቅ መቻል ይኖርብኛል፡፡ ስንስቅ ፍርሐት አቅሙ ቀነስ ይልና ምናልባት ወደ ፍቅር የመሄጃ የማርያም መንገድ ሊሰጠን ይችል ይሆናል፡፡
ትሩማን ካፖት (Truman capote) የተባለ አሜሪካዊ ደራሲ “የገና ትዝታ” የምትል ምርጥ አጭር ልብወለድ አለችው፡፡ ልብ ወለዱ ውስጥ አንድ የመጠጥ ቤት ባለቤት የሆነ ሰውዬ አለ፡፡ ሰውየው በጣም ጨፍጋጋ ፊት ያለው፣ አንድ ቀንም ሲስቅ ተሰምቶ የማያውቅ አይነት ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዚህ አስፈሪ ፊት ላለው ሰው “ha-ha” የሚል ስም አወጡለት፡፡ ስቆ ለማያውቅ ሰው የሳቅ ድምፅ ቅላፄን ስም ብለው ሰጡት፡፡ ስሙ ተጣበቀበት፡፡ እና ካፖት የሰውየውን ገፅታ ገልፆልን እየፈራነው እያለ ስሙን ሲነግረን ቀለል ይለናል፡፡ ገፀ ባህሪው በስሙ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም መልኩ የሚያስፈራ ግን መልካም ሰው ሆኖ የተቀረፀው፡፡
የፍርሐት መንፈስ የነገሰባት ሀገር ላይ የሳቅ ት/ቤት መኖሩ ደስ ይለኛል፡፡ ት/ቤቱ እንደሌላው ትምህርት ቤት የትምህርት ጥራት የጐደለበት እንዳይሆን ምኞቴ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት ሲጎድል በግድ የሚስቁ ምሩቃን….መፍትሔ የማይፈጥሩ እንዳይሆኑ እሰጋለሁ፡፡ መፍትሔው ሳቅ ነው፡፡ ከበድ ተደርገው የሚታሰቡትን ነገሮች ትንሽ ቀለል አድርጐ ክብደታቸው ልንሸከማቸው ከምንችለው መጠን በላይ እንዳይሆን ማበጀት፡፡
“የቡድን መብት ከግለሰብ መብት ይቅደም”፤ ግዴለም…ለግለሰብ ግን የመሳቅ መብት ይፈቀድ፡፡ ለመሳቅ ምክንያት ያስፈልጋል፡፡ ለመሳቃችን ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉት ደግሞ ፍርሐቶቻችን ናቸው፡፡ የግብር ፍርሐት አለብን፣ የእውቀት ፍርሐት፣ የእውነት ፍርሐት፣ መሪን የማምለክ ፍርሐት፣ የነፃነት ፍርሐት…ወዘተ፡፡ ቀልድ እና ሳቅ ግትርና ተወጥሮ ላይበጠስ የሚያጨናንቀን መንፈሳችንን ረገብ ካላደረገው … ህልውናችን ትርጉም የለውም፡፡ ሰው ለመሆን ሰውነትን ማጣት ነው ነፃነታችንን የሚነፍገን፡፡
የጥንት ሰው ሰማዩ አልደርስ ወይ አልገሰስ ሲለው ሳይሆን አይቀርም የፍጥረትን ረቂቅ ሚስጥር ራሱ በፈጠረው ቀልድ ረገብ ለማድረግ የሚሞክረው፡፡ እናም፤ ምድር እና ህዋ የሰባት ቀናት የፈጣሪ ሳቅ ውጤት ናቸው ብሎ ተረተ፡፡ የሰባተኛው ቀን የሳቅ ውጤት ደግሞ ራሱ ሰው ነው ይለናል - ተረቱ፡፡ ምናልባት ሃይማኖት በጣም ከሮ የሚሆነውን ሲያጣ ሊሆን ይችላል የቀልድ ፈጣሪው በራሱ አስመስሎ ወደ ፈጣሪ ጆሮ እቺን “ጆክ” ያስወነጨፋት፡፡ ምናልባት ፈጣሪ ፈታ ብሎ ስቆ ከፈጠረኝ፣ የእኔ ሌት ተቀን መጨነቅ የት ለመድረስ ነው? እንደማለት፡፡ ፈጣሪ በሳቅ ከሆነ ሰውን የፈጠረው…ሰው ተፈጥሮ ላይ ወይንም ራሱ ስቆ ማስተጋባት እንጂ… ማልቀስ ሞኝነት መሆኑንም ያስታውሰናል፡፡ ፈጣሪ በራሱ ቀልድ የሚስቅ ከሆነ ሞኝነት ሰማይና ምድርን የሚያስተሳስረው ብቸኛው ምስጢር ሳይሆን አይቀርም፡፡  ግን ክርስቶስ የአምላክን ባህርይ ለብሶ ስቆ ያውቅ እንደነበረ ብጠራጠርም፣ የሰውን ስጋ ሲለብስ ግን አልቅሷል፡፡ እየወደቀ እየተነሳ መስቀሉን ተሸክሞ ሲጓዝ የሳቁበትም ነበሩ፡፡ በሳቃቸው ስቃዩን ዝቅ አድርገው፣ በዛች ቅፅበት ፍርሐታቸውን መርሳት ችለዋል፡፡ የራሳቸውን የሞት ፍርሐት መሲሁ ከወረደበት ተመልሶ ሲወጣ የሳቁበተ ላይ ይስቅባቸው ይሆን?...ያስፈራል፡፡ እያስፈራም ግን በውስጡ አንድ ኮሜዲ ከጥቀርሻው የሰው ልጅ እጣ ፈንታ ውስጥ አራግፎ መፍጠር እና ጊዜያዊ እፎይታ በሳቅ ውስጥ ማግኘት ሳይሻል አይቀርም፡፡
ሳቅ የሰው ልጆች አንጡራ ሀብት መሆኑን አምናለሁ፡፡ ጨለም ያለ መንፈስ በተጫነኝ ጊዜ ለጨለምተኛ መንፈስ ከብርሐን ይልቅ ሳቅ የበለጠ ተስፋን ይፈነጥቃል፡፡  

Published in ህብረተሰብ

አቶ ሙሼ ሰሙ
(የቀድሞ የኢዴፓ ሊቀመንበር)

    አዲስ አድማስን በሶስት መሠረታዊ አቅጣጫዎች የማየው፡፡ አንደኛ ፈር ቀዳጅ ጋዜጣ ነው፡፡ በተለያዩ አምዶቹ የተለያዩ አጀንዳዎችን፡- ማህበራዊ፣ ስፖርት፣ ጤና፣ ኪነጥበብ፣ ፖለቲካና የመሳሰሉት ጉዳዮችን አካትቶ የሚወጣ ጋዜጣ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የተሟላ ገጽታ ይዘው መውጣት ከጀመሩ ጋዜጦች ቀዳሚው ነው፡፡ ብዙዎቹ ሲጀምሩ ዋነኛ ጉዳያቸው ፖለቲካ ብቻ ነበር፡፡ ቋሚ አምደኛ የሚባለው ነገርም ብዙ ጊዜ ከአዲስ አድማስ ጋር የመጣ ባህል ነው። ቋሚ አምደኛን ለረጅም ጊዜ ማሳተፍ በሌሎች ሀገሮች የተለመደ ነው፡፡ በ97 ዓ.ም ከተፈጠረው መንገራገጭ ውጪ አብዛኛውን ጊዜ ጋዜጣው በተቻለው መጠን ሚዛናዊና ምክንያታዊ ለመሆን ጥረት ሲያደርግ አያለሁ።
ሁለተኛው ፈር ቀዳጅ ነው የሚያስብለኝ በሌሎች ጋዜጦች ላይ የሚደርሰው ፈተና ሁሉ በዚህ ጋዜጣ ላይ አይደርስም የሚል እምነት የለኝም፡፡
የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ተግዳሮት የሚያጋጥመው ከመንግስት ብቻ አይደለም፡፡ በመንግስት ውስጥ የተቀመጡ ባለስልጣኖችም የተግዳሮት ምንጭ ናቸው። ያንን ሁሉ ተቋቁሞ ላለፉት 15 አመታት ሣይቋረጥና ሣያጓድል መውጣቱ በጣም ትልቅ ፈር ቀዳጅነት ነው ብዬ አምናለሁ።
ይሄ ደግሞ የምክንያታዊነት ውጤት ነው። ሽያጩ ጨመረ ቀነሰ ሳይባል የፖለቲካው ትኩሳትና መቀዛቀዝን ሳይከተል ወጥነትን ይዞ መሄዱ አንዱ ፈርቀዳጅነት ነው፡፡
ሌላው በህዝቡ ዘንድ ባለው ተቀባይነት በጣም ወጥቶ ወይም ወርዶ ያየሁበት ሁኔታም አልነበረም፡፡ ይሄ እንግዲህ ለአንድ ጋዜጣ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በቋሚነት አንባቢ ያለው፣ በትክክል ስነልቦናውን ተረድቶ መልዕክቱን ማስተላለፍ የቻለ ጋዜጣ ነው ብዬም አስባለሁ፡፡ ከነዚህ አኳያ አዲስ አድማስ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ የራሱን ደንበኞች መፍጠር የቻለም ጋዜጣ ነው፡፡
ወደፊት፣ ይሄን ተቀባይነቱን ተጠቅሞና አድማሱን አስፍቶ፣ ሌላውን ማህበረሰብ መድረስ የሚያስችል ውጥን ያስፈልገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በፖለቲካ ጉዳይ ላይ ሠፋፊ ሃተታ የመፃፍ ጉዳይ ብዙም አይታይም፤ ለዚህ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ ሠፋ ያሉና ጥልቀት ያላቸው ፅሁፎች የሚያስተናግድበት ሁኔታ ሊታሰብ ይገባል፡፡ እንደ ተቋም፤ በእነዚህ 15 አመታት ግዙፍና ሠፊ መሆን መቻል ነበረበት፡፡ ያንን መፍጠር ያስፈልጋል። በቂ አቅም ሲፈጥር ተፅዕኖ መቋቋምና ስራውን በነፃነት መስራት ይችላል፡፡

Published in ዜና

    “ከወፍራም ቡና ጋር አብሮ የሚሄደው ነገር ምንድን ነው?” ብዬ ስጠይቃችሁ፤ ምን ቡና አለ?! ብላችሁ ወደ ወትሮው ምሬታችሁ እንድትገቡ አልፈልግም፡፡ ከወፍራም ቡና ጋር የሚሄደው ነገር ንባብ ነው፡፡ ጋዜጣ ወይንም መፅሔት አሊያም መፅሐፍ ከያዛችሁ ማለፊያ ነው፡፡ … ታዲያ ቡና እያጠጣ ጋዜጣ በራሱ ሂሳብ ገዝቶ አንብብልኝ የሚል ካፌ ከተገኘ ይኼ ሰው ባለውለተኛነቱ … ለቡና ጠጪ እና ለንባብ ፈላጊ ብቻ ሳይሆን … ከንባቡ ጀርባ ላሉት የጋዜጣና መፅሔት ፀሐፍት (የፃፉት እንዲነበብላቸው ለሚፈልጉ) እንዲሁም ለቡና ገበሬዎችና ቡና ነጋዴዎች (ያመረቱት እንዲጠጣላቸው ለሚመኙትም) ጭምር ነው፡፡ ቡናን ፉት እያሉ ንባብን ማጣጣም የሚችሉበትን ካፌ ገርጂ ያገኙታል፡፡
የመብራት ኃይል ካፌ ባለቤት አቶ ፀጋዬ ወንድሙ ራሳቸውን ያስተዋውቁንና ስለ ካፌያቸው ያወጉናል፡፡  

ፀጋዬ ወንድሙ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት እዚህ አዲስ አበባ ለገሀር አካባቢ ነው፡፡ በስፖርት ውስጥ በሩጫ እሳተፍ ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ ወደ ውጭ የመሄድ አጋጣሚ ፈጠረልኝና ወደ ጣሊያን አመራሁ፡፡ ጣሊያን ለሁለት አመት ያህል ከቆየሁ በኋላ ወደ ካናዳ ተሻገርኩ፡፡ እዚያም ለ14 አመታት ኖርኩ፡፡ ካናዳ በነበረኝ ቆይታ በሩጫው ዘርፍ እወዳደር ነበር፡፡ በመጨረሻ ከ8 አመት በፊት ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ካፌ ከፍቼ መስራት ጀመርኩ፡፡
ካናዳ ምን እየሰራህ ነበር የምትኖረው?
ያው መጀመሪያ በሩጫው ምክንያት ነው ከሀገር የወጣሁት፡፡ ካናዳ ከሄድኩኝ በኋላም አንድ ድርጅት ወክዬ እሮጥ ነበር፡፡ ነገር ግን የካናዳ የአየር ንብረት ትንሽ ስለከበደኝ በሩጫው መቀጠል አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ሰው የተለያዩ የዕለት ተእለት  ስራዎችን እየሰራሁ ለ14 አመት ቆየሁ፡፡ የካናዳ ዜግነት ስላለኝ በፈለግሁት ጊዜ በመመለስ መኖር እችላለሁ። ነገር ግን ወደ አገሬ ስወጣ ለራሴም ገቢ የሚፈጥር፣ ህብረተሰቡንም የሚያግዝ ሥራ መስራት አለብኝ ብዬ ስለሆነ እየሰራሁ ነው፡፡
ከካናዳ መጥተህ እንዴት የካፌ ስራ ውስጥ ገባህ?
ከልጅነቴ ጀምሮ በተለያዩ ቢዝነሶች የመሰማራት እድሉ ነበረኝ፡፡ ሞተር ብስክሌት እና መኪና አለማምድ ነበር፡፡ መኪና ወደ ካፌ ቢዝነስ ልገባ የቻልኩት ግን  በካናዳ ባሳለፍኳቸው ጊዜያት ከጓደኞቼ ጋር እየተገናኘን የተለያዩ ነገሮችን የምንወያየው በካፌ ውስጥ ነበር። ካፌ ውስጥ ገብተን ጓደኞቻችንን በምንጠብቅበት ወቅት ታዲያ የእለቱን ጋዜጦችና መጽሔቶች ካፌው ያቀርባል ቴሌቪዥንም ይከፍታል፡፡ ወጣቶችም ይሁኑ አዛውንቶች ወደዚህ ካፌ ሲመጡ ከህትመት ውጤቶች ላይ መረጃዎችን እንዲያገኙ እፈልጋለሁ፡፡ ወጣቶች በተለይ አጓጉል ቦታ ጊዜያቸውን ከማሳለፍ እዚህ እያነበቡ፣ ቴሌቪዥን እየተመለከቱ የሚቆዩበት መንገድ ተመቻችቷል፡፡ ሥራ ፈላጊዎች ሳይጉላሉ ከጋዜጦች ላይ ክፍት የሥራ ቦታዎችን ያያሉ፡፡ እዚህ ክፍት የስራ ቦታ አይተን ስራ አገኘን የሚሉ ብዙ ደንበኞች ያጋጥሙኛል፤ ይሄ ያስደስተኛል፡፡
ከካፌ ሌላ ቢዝነስ አለህ?
በትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ እየሰራሁ ነው።  ገልባጭ መኪኖች አሉኝ፡፡ ከሚኒባስ ስራ ነው ወደ ገልባጭ የቀየርኩት፡፡
የየዕለቱን ጋዜጣ በማቅረብህ የካፌ ሥራህ አልተጐዳም? ደንበኞች ጋዜጣ ሲያነቡ ለረዥም ሰዓት መቀመጫ ይይዛሉ ብዬ ነው……
ለገንዘብ ብዬ የሠውን ፍላጐት መጫን ስለሌለብኝ ደንበኞቼ እንዲያነቡ ፈቅጃለሁ፡፡ መፍቀድ ብቻ አይደለም፤ የሚያነቡትንም እያቀረብኩ ነው፡፡ ያለምንም የሰአት ገደብ ማንበብ ይችላሉ፡፡ ይህንን ሳደርግ እኔም የማገኘው ጥቅም አለ፡፡ ሰው ጋዜጣ ለማንበብና ክፍት የስራ ቦታዎችን ለማየት ሲል ከተለያዩ ሰፈሮች ወደ እዚህ ካፌ ይመጣል፡፡ ጋዜጣውን ለማንበብ ሲቀመጥ ደግሞ ማዘዙ አይቀርም፡፡ ስለዚህ አንድ ደንበኛ የመሳቢያ መንገድ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ጋዜጦችን ማቅረቤ ለቢዝነሱ የሚሰጠው ጥቅም አለ ማለት ነው…
በብዙ ካፌዎች ግን እንዲህ ያለ ነገር አልተለመደም። እንደውም “ጋዜጣ፣ መፅሐፍ ማንበብ ክልክል ነው” የሚሉ ማሳሰቢያዎች የሚለጥፉ ሁሉ ያጋጥማሉ፡፡
እንግዲህ ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ ፍልስፍና፣ የራሱ የሆነ አተያይ ይኖረዋል፡፡ እነዚያ ሰዎች ለምን እንደዚያ እንዳደረጉ አላውቅም፡፡ እኔ ግን ባለኝ እውቀትና የአስተሳሰብ ደረጃ አንድ ሰው መረጃ ማግኘት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ እየተከናወኑ ያሉ አዳዲስ ነገሮችን ሊያውቅና መረጃው ሊኖረው ይገባል የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ከሬዲዮና ከቴሌቪዥን ከሚያገኘው መረጃ ባሻገር ከተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች አዳዲስ መረጃዎችን እያገኘ፣ እግረ መንገዱን የማንበብ ባህልን እያዳበረ እንዲሂድ ባለኝ ፍላጐት ነው ይህንን ተግባር እያከናወንኩ ያለሁት፡፡
በካፌው ውስጥ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲነበቡ በማድረግህ ምክንያት የገጠመህ ቅሬታ ወይ ትችት አለ?
በሁኔታው የሚደሰቱ እንዳሉ ሁሉ የሚከፉ ሊኖሩ የሚችሉበት አጋጣሚ አለ፡፡ እኔ ግን አምኜበት የማደርገው ስለሆነ “እገሌ ስለከፋው ማስነበቤን ላቁም” የምልበት ምክንያት አይኖረኝም፡፡ የሚደሰተውን እያስደሰትኩ መቀጠል ነው የኔ ሃላፊነት፡፡
ሰው አንድ ጋዜጣ ገዝቶ ሊያነብ ይችላል፤ ነገር ግን ሁሉንም የየዕለቱን ጋዜጣ ገዝቶ ሊያነብ አይችልም፡፡ ያንን ለማድረግ የኑሮውም ሁኔታ ላይፈቅድለት ይችላል፤ ስለዚህ እኔ ሁሉንም የየዕለቱን ጋዜጦች በማቅረብ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ለህብረተሰቡ በመፍጠር ከሌላው አለም ያገኘሁትን ተሞክሮ በአቅሜ ለዚህ ህብረተሰብ እያካፈልኩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ለምን ጋዜጣ ታስገባለህ ተብዬ የተጠየቅሁበት ጊዜ ሁሉ አለ፡፡ ሰው ቁጭ ብሎ ሲያነብ ችግር ለመፍጠር የተሰባሰበ ወይም ተቃውሞ ሊመስል ይችላል፡፡
በዚህም ምክንያት በተለያዩ አካላት ጋዜጣ እንዳላስነብብ ተነግሮኝ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ጋዜጦችን ሳመጣ መርጬ እንደማላመጣና ሁሉንም አይነት ጋዜጦች እንደማመጣ፣ ዓላማዬም ህብረተሰቡ መረጃ እንዲያገኝና የማንበብ ባህል እንዲያዳብር መሆኑን፣ ይሄም ከውጭ አገር ያገኘሁት ተሞክሮ እንደሆነ አስረድቻቸዋለሁ፡፡  
ከህብረተሰቡ ምን አይነት ምላሽ ታገኛለህ?
ህብረተሰቡ በጣም ደስተኛ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ሄጄ ባጋጣሚ ጋዜጣ ተከራይቼ በማነብበት ወቅት የተለያዩ ሰዎች የኪራዩን ሒሳብ የሚከፍሉበት ጊዜ አለ፡፡ እኔ በመልክ እንኳን የማላውቃቸው ሰዎች “አንተ ሁሌ በነፃ እያስነበብከን እኛ የአንድ ቀን የጋዜጣ ኪራይ ብንከፍል ምን አለበት” ይላሉ፡፡ በካፌ ውስጥ ቁጭ ብለው የሚያነቡ አዛውንቶች ሲመርቁኝ ህብረተሰቡ በዚህ ተግባሬ በጣም ደስተኛ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ አንዳንዴ እንደውም “እዚህ ስናነብ ባገኘነው ክፍት የስራ ቦታ አመለክተን ስራ አገኘን፤ ደስ ብሎናል ካልጋበዝኳችሁ “የሚሉ ደንበኞች ሁሉ ያጋጥሙናል፡፡ ስለዚህ በምንሰጠው አገልግሎት ህብረተሰቡ ደስተኛ ነው ብለን እናምናለን፡፡
አንዳንዶች የተሻለ ደሞዝ ያለው ሥራ ማግኘታቸውን ሲነግሩንም ደስ ይለናል፡፡ ለካ እንዲህ እያደረግን ነው ብለን እንድናስብ የሞራል ድጋፍ ይሆነናል፡፡
በአንተ ተሞክሮ በህብረተሰቡ ውስጥ የማንበብ ባህል አለ ብለህ ታስባለህ?
እኔ እንዳየሁት ከሆነ አቅሙ እስካለውና ሁኔታዎች ተመቻችተው እስከቀረቡለት ድረስ ህብረተሰቡ የማንበብ ፍላጐት አለው፡፡ ማታ ካፌውን በምንዘጋበት ሰአት መጥቶ 10 ደቂቃ ለንባብ ብሎ የሚያስፈቅድ ደንበኛ ሁሉ አለ፡፡ ይሄ ህብረተሰቡ የማንበብ ፍላጐት እንዳለው ያሳየኛል፡፡ ሌላው የመግዛት አቅሙ ባይኖረው እንኳን ተከራይቶ ሲያነብ ይስተዋላል፡፡ ከሰው ከሚሰማው ነገር ይልቅ አንብቦ ለመረዳት ያለው ፍላጐት ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ እንደኔ አስተያየት ህብረተሰቡ የማንበብ ፍላጐት አለው ነው የምለው፡፡ እንደዚያ ካልሆነማ፣ ለምን የተለያዩ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን እየገዛሁ አስቀምጣለሁ? ሌላው ቀርቶ ስንዘጋ አንብቦ ያልጨረሰ ደንበኛ ካለ፣ ቤት ወስጄ ላንብብና ጠዋት ልመልስ የሚልበት አጋጣሚ ሁሉ አለ፡፡
ጋዜጣ ለምን ታስነብባለህ የሚል ጫና አሁንም ይደርስብሃል?
እኔ በግልፅ ተናግሬአለሁ፡፡ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ዓላማ እንደሌለኝና ለሥራ የቆምኩ መሆኔን፣ ጋዜጣ አታስነብብም ከተባልኩ ካፌውንም እንደምዘጋ ገልጬአለሁ፡፡ እነሱም አንባቢው ጤነኛ እንደሆነና ምንም አይነት ችግር እንዳልተፈጠረ ሲያዩ ትተውኛል፡፡  አሁን ምንም አይነት ጫና የለብኝም፡፡ ይሄም የሆነው ሥራ የጀመርኩ ሰሞን ብቻ ነው፡፡
በልጅነትህ የማንበብ ልማድ ነበረህ?
ከልጅነቴ ጀምሮ የማንበብ ባህሉና ፍላጐቱ ነበረኝ ልልሽ አልችልም፡፡ የማንበብም ሆነ የማስነበብ ባህልን ያዳበርኩት ውጪ በነበርኩበት ጊዜ ነው፡፡ ለምሳሌ ካናዳ ስኖር የማስተውላቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ በየካፌው የተለያዩ መጽሔቶች እና ጋዜጦች ተደርድረው ለደንበኞች ይቀርባሉ፡፡ እነሱ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው በመረጃ የተደገፈ ነው፡፡ ስለዚህ የንባብ ነገር ካናዳና ጣሊያን በነበረኝ ቆይታ ያዳበርኩት ባህል እንጂ ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረ አይደለም፡፡
የየዕለቱ የጋዜጦች ወጪህ ስንት ነው?
በየቀኑ የሚወጡትን ሁሉንም አይነት ጋዜጦች አመጣለሁ፡፡ በቀን ለጋዜጣና ለመጽሔት እስከ 50 ብር አወጣለሁ፡፡ በሳምንት እስከ 350 ብር ገደማ ይሆናል። ለአንድ አስተናጋጅ በወር የምከፍለውን ደሞዝ ማለት ነው፡፡    

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ለአድማሶች፣ እንኳን ለአሥራ አምስተኛ ዓመታችሁ አደረሳችሁማ!
“እንኳን ለምናምነኛ ዓመት አደረሳችሁ…” መባባል አሪፍ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ለመባል ዕድሉን ያላገኙትን ማሰቡ ጥሩ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ጥያቄ አለን፣ በ‘ድሮ አራድነት’ና በ‘‘ዘንድሮ አራድነት’…አለ አይደል…ፊልሞች ይሠሩልንማ! ልክ ነዋ…ነገሮች ግልጥና ግልጥ ይሁኑልና! የአራዳነት ‘ዴፊኒሽን’ ተለውጦ ከሆነም ይገለጥና መቀመጫ ሳጥናችንን እንወቅማ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የድሮ እንትና የድሮዋን እንትናዬን ለማጥመድ የነበረው ‘ውጣ ውረድ!’ ልጄ ዘመን ተለወጠና ስሟን ሳያውቅ ‘እሷን የሚያውቅበት’ ጊዜ ላይ ደርሰነው አረፍን! ቂ…ቂ…ቂ…  
እናላችሁ… በፊት አስቀድሞ ስሟ፣ የማን ልጅ እንደሆነች፣ ‘ጉልቤ ብራዘር’ ይኑራት፣ አይኑራት… ምናምን ይጠናል፡፡ ቀጥሎ በርቀት በ‘ዓይኑካ’ መከታተል አለ…ከዛ ‘መመኘት’ በህልም ማየት ምናምን አለ፣ ቀጥሎ ብጣሽ ወረቀት በትንሽ ልጅ አስይዞ መላክ አለ፣ መልስ መጠበቅ አለ…(እንደዛም ሆኖ እኮ ላይሳካ ይችላል!) “እሺ…” የተባለ ቀን…ምን አለፋችሁ… የሆነ ‘ኖቤል’ ምናምን ቢያሸንፍ እንኳን እንደዛ ደስ አይለውም፡፡ ደግሞ እኮ እሺታው ‘ሻይ ለመጠጣት’ ብቻ ነው፡፡ በድሮ አራዶች ሻይ እንጠጣ ማለት ሻይ እንጠጣ ነው፡፡ እና ዘቢብ ኬክና ቡና በወተት ሳይጋብዝ ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሻገር!
ከዛላችሁ…ከተወሰኑ ሳምንታት የዘቢብ ኬክና… አለ አይደል… እንደ እሱዬው ‘ኤኮኖሚክ ስታተስ’ ከባቅላባ ግብዣ በኋላ ደግሞ ጉዞ ሐምሌ አሥራ ዘጠኝና፣ ብሔረ ጽጌ ይሆናል፡፡ እሱኛው የፐሮጀክት ፌዝ ቂ…ቂ…ቂ… ለመጠናቀቅ ወራት ሊፈጅበት ይችላል፡፡ ‘ተጠናቀቀ’ የሚባለው …‘ኪሶሎጂ’ (ያውም ‘በስሱ’!) ላይ ሲደረስ ነው፡፡ በድሮ አራድነት እንደ ነብር ዘሎ መከመር የለማ! ቂ…ቂ...ቂ.
ከዛ ምን አልባት ከአሥራ አንድ ወር ምናምን በኋላ… “ለምን ብቻችንን…” ምናምን ይባላል፡፡ ዕድሜ ለሦስት ብር…. ከሰፈር በሁለት አውቶብስ ወደሚኬድበት አካባቢ ጉዞ ይሆናል፡፡ ልክ ነዋ… የሰፈር ሰው፣ የሂሳብ ቲቸር፣ የጓደኛ እህት…ምናምን እንዳያዩ ይፈራላ! እንደ ዘንድሮ… ወላጆች ራሳቸው እንትንዬው በር ላይ አድርሰው… “በሉ ይቅናችሁ…” ብለው የሚመለሱ የሚመስልበት ዘመን አልነበረማ!
ከተገባ በኋላ መጀመሪያ እንጨት ወንበሩ ላይ፣ ቀጥሎ ‘ቤዱ’ ጫፍ…ምናምን እየተባለ እየተዳኸ መሀል ይደረሳል፡፡ እናላችሁ… እንዲህ፣ እንዲህ እየተባለ ‘ዓይን ይበራል!’
(እነ እንትና…ያ በብርጭቆ ወረቀት ተፈግፍጎ ከፋይ ይመስል የነበረው የወታደር ጫማ እስኪወልቅ የሚፈጀው ጊዜ ትዝ ይላችኋል! እኛ የቻይና ሸራ እናደርግ ስለነበር እናውቀውም! ቂ…ቂ…ቂ…)
እንደ ዘንድሮ ቢሆን ከነጠላ ጫማ የማትሻል ጫማ ነገር ያለካልሲ ጠለቅ አድርጎ… በእጅ ‘ተፈታ፣ አትፈታ’ ብሎ መታገል አያስፈልግም፡፡ እግርን ወርወር ሲያደርጉት ጫማዋ ተስፈንጥራ ትወልቃለቻ! ጊዜ የለማ! ‘ሌላዋ ተረኛ’ ብሔራዊ ትያትር አካባቢ ‘ወክ’ እያደረገች ሊሆን ይችላላ!
የምር ግን…አለ አይደል…ዘንድሮ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በቃ ሰዉ ‘የናሽናል ጂኦግራፊ’ ዘጋቢ ፊልም ከልክ በላይ የሚያይ ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ…ፊልሞቹ ላይ እንደምናያቸው አንበሶችና ነብሮች ‘ዘሎ ጉብ’ ሆኗላ!
የያኔው ‘ፕሮጀክት’ ከመስከረም እስከ ነሐሴ፣ የዘንድሮ ‘ፕሮጀክት’ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ!
“እንኳን ለምናምነኛ ዓመት አደረሰህ!” ለመባል ያብቃንማ!
የምር ግን…
አፈረሱት አሉ ውቤ በረሀን
እንደ እናት እንደ አባት ያሳደገንን፤
ዘፈን ብቻ መሆኗ ቀርቶ እውነት ሆነች አይደል! የፈረሰው ጣራና ግድግዳ ብቻ አይደለማ! የፈረሰው ‘ዘመን’ ነዋ!
አንዱንም በቴስታ ነበር ልማዳችን
አንዱንም በካልቾ ነበር ልማዳችን
ሚስት አገባንና
ልጆች ወለድንና
ፈሰሰ ሀሞታችን፤
ይባልበት የነበረበት ዘመን፡፡ የ‘ቤዱ’ ብቻ ሳይሆን የ‘ቡጢው’ ትውስታ ታትሞ የሚቀርበት ዘመን!
ዘንድሮ ልጄ ‘ሜሞሪ’ ሲባል የሚታውቀው የ‘ሞባይል ሜሞሪ’ ነው፡፡ ልክ ነዋ…መዝናኛዎቹ ከእነ ስማቸው እኮ…ቺቺኒያ!  እኔ የምለው እስካሁን ምነው ለቺቺኒያ ‘ፖፑላር’ የሆነ ነገር አልተዘፈነላትም!
ስሙኝማ…ቺቺኒያን ካነሳን አይቀር… የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…በአንዳንድ አውሮፓ አገሮች የቀለጡት መንደሮቻቸው ውስጥ የነገርዬው ‘ዊንዶው ሾፒንግ’ ነገር አለ አሉ፡፡ በቃ በ‘ዊንዶው’ በኩል አይቶ ‘በል፣ በል’ ካለው በ‘ዶሩ’ በኩል ይገባላ! አንድ ወዳጄ ሲነግረኝ…ሌሊቱ ሲገፋ ቺቺኒያ ውስጥ አንዳንድ ቤቶች በሮቻቸው እስከመጨረሻ ይከፈቱና እንትናዬዎቹ ፊት ለፊት በሚያስደነግጥ አቀማማጥ እንደ ‘ዓውደ ርዕይ’ አይነት… ብቻ ተዉት! ነገርዬው ግን… “እንደው የት እንደርስ ይሆን!” የሚያሰኝ ነው፡፡
“እንኳን ለምናምነኛ ዓመት አደረሰህ!” ለመባል ያብቃንማ!
እንግዲህ ደጃች ውቤ ምን አገር ሆነች
ያቺም ልጅ አገባች፣ ያቺም ልጅ ሄደች፤
ይባልበት የነበረ ዘመን፡፡
በዛሬዋ ቺቺኒያ… አለ አይደል… “ያቺም ልጅ አገባች፣ ያቺም ልጅ ሄደች…” ብሎ ነገር የለም፡፡ ልክ ነዋ…‘እነሆ በረከት’ በተባባሉ በአራተኛው ቀን… “ይቺን ልጅ የሆነ ቦታ አውቃታለሁ…” መሰለኝ… አይነት ነገር ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…
በአሥራ አምስት ዓመቷ ትገኝ በነበረች
እንደ ዳማ ከሴ መድኃኒት ነበረች፣
የተባለበት ዘመን አይገርማችሁም! ዘንድሮ ግን እንትናዬዎች በ‘ፊፍቲና በፊፍቲ ፋይቭም’…አለ አይደል…‘ዳማ ከሴ’ እየሆኑ ነው፡፡ ጊዜው ተለውጧላ! ቂ…ቂ…ቂ…  የተውኔትና የሲኒማ ሰዎች ‘የባለ ፊፍቲ ፋይቮቹን’ ዳማ ከሴዎች… አለ አይደል… የአሥራ አምስቷን ገጸ ባህሪይ ‘በእውን የተላበሱ’ ይሏቸው ነበር፡፡ (እነ እንትናዬ…ፊፍቲ ምናምን አልደረሳችሁም ብዬ ነው ‘እንደ ልቤ’ የምናገረው!)
እናላችሁ…
አደገች አደገች በቀሚሷ ሞላች
የእኔን የድሀውን አንጀት እየበላች፤    
አይነት ከወዲሁ ‘አፕሊኬሽን’ የሚገባበት ዘመን ነበር። እንደ ዘንድሮ ‘ሃራስመንት’ ምናምን የሚባሉት ቃላት ያልታወቁበት ዘመን ነበራ! እኔ የምለው… እነ እንትና… “ሽንኩርት ነች…” ይባል የነበረው ምንን ለመግለጽ ነው! ልክ ነዋ… እኛ ሽንኩርት የምናውቀው ሲከትፉት ዓይን እንደሚያቃጥል ነዋ!
እናላችሁ…ዘመን ሲለወጥ፣ ጊዜ ሲገሰግስ፣ ‘ኤጅ’ም እየጨመረ ሲሄድ…ክፉው ነገር እየቀረልን ደጉ ነገር እየተያዘ ይቀጥልልንማ! ጊዜ ክፉውን ጥሎ፣ ደጉን ይዞ ይቀጥልልንማ!
ለአድማሶች፣ እንደገና…እንኳን ለአሥራ አምስተኛ ዓመታችሁ አደረሳችሁማ!
“እንኳን ለምናምነኛ ዓመት አደረሰህ!” ለመባል ያብቃንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ህብረተሰብ

     በቅርቡ “ሉአላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባወጡት መፅሐፍ የመጀመርያዎቹ አራት ምዕራፎች ላይ ራስዎንም ጭምር እየተቹ ፅፈዋል፡፡ የ1993 ክፍፍልና ከዚያ በኋላ ያለውን በሚተርከው ክፍል ላይ ግን ብዙ የተድበሰበሱ ጉዳዮች እንዳሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ….
እኔ ይሄን መጽሐፍ በሁለት አላማዎች ነው የፃፍኩት። አንዱ አላማ በኢትዮጵያ የሉአላዊነት ጉዳይ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ማስገንዘብ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሂደት በ40 አመት ውስጥ ከየት ወዴት እንደደረሰ ለማሳየት ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች ይሄን ግንዛቤ እንዲይዙ ከራሴ ልምድና ከነበርኩበት ድርጅት አጠቃላይ እንቅስቃሴ በመነሳት የተቻለኝን ሁሉ አስቀምጫለሁ የሚል አስተያየት አለኝ፡፡
እኔ መጽሐፉ ከወጣ በኋላ ከደረሱኝ አስተያየቶች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ነገሮችን በግልጽ ማስቀመጤን የሚጠቁ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዱ ከሚጠበቀው በላይም ተገልጿል የሚል ነው፡፡ በህወሐቶች ዘንድ ደግሞ አላስፈላጊ የሆኑ ሚስጥሮች አውጥቷል ተብሎ እንደሚታሰብ ተገንዝቤአለሁ፡፡ እኔ ግን ህሊናዬና አቅሜ በሚፈቅደው የተቻለኝን ያህል እውነታውን ገልጨዋለሁ፡
በግልፅ አልተብራራም ከተባሉት መካከል በ1993 ክፍፍል ወቅት እርስዎን ጨምሮ አቶ ስዬ፣ አለም ሠገድ፣ አባይ ፀሐዬ… በአቶ መለስ ቦናፓርቲዝም ዙሪያ ያቀረባችሁት ጽሑፍ በሚገባ አልተጠቀሰም የሚለው ይገኝበታል፡፡ ምን አይነት ጽሑፎች ነበሩ የቀረቡት?
በኔ በኩል ስለ መለስ ቦናፓርቲዝም በመጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር አስቀምጫቸዋለሁ፡፡ የመለስ አቋም፤ በኢትዮጵያ አመራር ውስጥ ቦናፓርቲዝም በግልፅ ተከስቷል የሚል ነበር፡፡ የቦናፓርቲዝም ዋናው ጉዳይ ደግሞ ሙስናና ፀረ ዲሞክራሲያዊነት ነው ብሏል፡፡ የኛ ጽሑፎች ከዚህ የተለዩ ናቸው፡፡
የቦናፓርቲዝም ንድፈ ሃሳብ መለስ ከአስቀመጠው የተለየ ትርጉም ነው ያለው፡፡ የቦናፓርቲዝም ዋናው ቁምነገር ሁለት ሃይሎች/መደቦች ለመጠፋፋት ከጅለው፣ ይሄን መጠፋፋት አስታርቆ የሚመጣ መካከለኛ መንግስት ማለት ነው፡፡ በመለስ አገላለጽ ግን ቦናፓርቲዝም ሙስናና ፀረ ዲሞክራሲ ስርአትን ለማንገስ የመጣ ስርአት ነው፡፡ ከዚያ በላይ በእኛ ፅሁፎች በስፋት የተገለፀው መለስ በወቅቱ የነበረውን የኢትዮጵያን ችግር በስፋት አላቀረበም የሚል ሃሳብ ነው፡፡ በወቅቱ ከነበረው ትልቅ ችግር ለመሸሽ የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው የሚል አቋም ነው የያዝነው፡፡ ምክንያቱም የወቅቱ ትልቁ የኢትዮጵያ ችግር የሉአላዊነት መደፈር ነው፡፡ በተለይ በኤርትራ መንግስት የተቃጣብን ወረራ በልማታችን ላይ ያስከተለውን ችግር ሣይናገር፣ ሌላ ጉዳይ አንስቶ ከዋናው አጀንዳ አፈግፍጓል ብለን ነው በጽሑፋችን ያስቀመጥነው፡፡ ሉአላዊነት ሲባል የድንበር ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ በሀገራችን፣ በህዝባችን፣ በመንግስታችን ላይ የተቃጣ መሆኑም ጭምር ነው። መለስና ጓደኞቹ ለውጭ ጫና ተንበርክከው፣ በወቅቱ ከእውነታው ሸሽተዋል የሚል ነው የጽሑፋችን ጭብጥ፡፡ እሱ ደግሞ ዋናው ጉዳይ የሙስናና የዲሞክራሲያዊነት ነው፤ የሉአላዊነት ጉዳይ ውጫዊ ጉዳይ ነው ብሎ ነው ያቀረበው፡፡ በአጠቃላይ አቶ መለስ ያቀረበው ጽሑፍ ከሉአላዊነት አጀንዳ የመሸሽ ነው፡፡
ከእናንተ ጋር አብረው አቶ መለስን ሲቃወሙ የነበሩት አቶ አባይ ፀሐዬ እንዴት ወደ አቶ መለስ ቡድን ተመለሱ?
ይሄን መመለስ ያለበት አባይ ራሱ ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ግን አቶ አባይ የመለስን አቋም ይቃወም ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተለይ ወረራውን በተመለከተ አቶ መለስ የወሰደው አቋም የተሣሣተ ነው በሚል ይቃወም ነበር፡፡ የእነ አቶ መለስ ቦናፓርቲዝም አስተሳሰብ ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የወጣና ያፈነገጠ ጉዳይ ነው ብሎ አጥብቆ ተከራክሯል፡፡ እንግዲህ የክፍፍላችን ሁኔታ የተጠናቀቀው በፖለቲካዊ ውይይት አይደለም፡፡ አቶ መለስ የሠራዊቱንና የደህንነቱን ጣልቃ ገብነት ተጠቅሞ ነው ያሸነፈው እንጂ በውይይት አላሸነፈም፡፡ አስቀድሞ ሠዎችን በመግዛት በማስፈራራት ነው ያሸነፈው፡፡ አባይም ምናልባት ይሄን ጫና መቋቋም አቅቶት ይሆናል እንጂ እስከመጨረሻው ያለውን ሃቅ ያውቀዋል፡፡
እስከመጨረሻው የክፍፍሉ ሰአት ድምፅም ሠጥቷል፡፡ ከታገዱት 12 ሰዎች ውስጥም አንዱ እሱ ነበር፡፡ የመለስን አቋም እቀበላለሁ ብሎ መግባቱ የመለስን ጫና መቋቋም አቅቶት ሊሆን ይችላል፡፡ በወቅቱ ውስጥ ገብቶ መታገል ነው የሚያዋጣው ብሎ ነበር፤ ከገባ በኋላ ግን እንዳለው አልታገለም፡፡ የህወሓት ችግር እየባሰበት ሄደ እንጂ የለወጠው ነገር የለም፡፡ ዋናው መልስ መስጠት ያለበት እሱ ቢሆንም የኔ መላምት በአቋሙ መዝለቅ ያቃተው ጫና በዝቶበት ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡
ግብርናን ኮሜርሻላይዝድ ለማድረግና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በሀገሪቱ እንዴት መተግበር እንደሚቻል የሚያመላክት የስትራቴጂ እቅድ ነድፈው ለአቶ አዲሱ ለገሠ ሰጥተው ነበር፡፡ ከዚያ እቅድ ውስጥ ኢህአዴግ እስካሁን ተግባራዊ ያደረገው አለ?
ብዙም አይመስለኝም፡፡ ያኔ አቶ መለስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ይቃወም ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ኢንዱስትሪው መምራት አለበት፣ ትላልቅ የመስኖ ስራዎች መተግበር አለባቸው፡፡ እርሻም መሠረቱን በሚለውጥ መንገድ መሄድ አለበት እንል ነበር፡፡ ከተሞችም በተጠና መንገድ ማደግ ነው ያለባቸው፡፡ ግብርና መር እያሉ እዚያው መንከባለል ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አያመጣም… የሚል አስተያየት ነበር ያቀረብኩት፡፡
በቅርቡ የ5 አመት እቅድ ብለው በነደፉት ላይ ኢንዱስትሪ መር እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ሁኔታው አስገድዷቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የሄዱበት መንገድ ለውጥ አለማምጣቱን ተረድተው ይሆናል፡፡ ሆኖም መሠረታዊ መዋቅራዊ ለውጥ እስካሁን ድረስ አልመጣም፡፡ ያኔ እነሱ የሚያዳምጥ ልቦና አልነበራቸውም፡፡ አሁንም የገቡበት ስትራቴጂ በተጠና መንገድ ስለመሆኑ ያሳብበኛል። የሆነ ሆኖ ያኔ የቀረቡት ሃሣቦች አሁንም አንዳንድ አሉ። እኔን ይበልጥ የሚያስገርመኝ ትግራይ ክልል ላይ እኛን ሲቃወሙን የነበረውን አሁን በእጥፍ እየተገበሩት መሆናቸው ነው፡፡ መለስ እኛን ለመምታት ሲል “ብክነት አለበት” ብሎ ያልተቀበላቸው የመስኖ ስራዎች፣ የመንገድ ስራዎች፣ የግድብ ስራ፣ የሪፈራል ሆስፒታል ስራ፣ የሠማዕታት ሃውልት ግንባታ… እነዚህን ሁሉ አሁን ትክክል ናቸው ብለው ተቀብለዋል፡፡ ይሄን ሲያደርጉ ደግሞ ያኔ ትክክል አይደሉም ላሉት ይቅርታ ሳይጠይቁ ነው፡፡ ለነገሩ እነሱ ከሠውም ወስደናል አይሉም፤ ይቅርታም አይጠይቁም፡፡ በኤርትራ ጉዳይ ብዙ ጥፋት ተሠርቶ ይቅርታ ያሉት ነገር የለም፡፡
ያኔ እናንተ “ሻዕቢያን ማንበርከክ…” ብላችሁ ያቀረባችሁት ሃሣብ ሊሳካ ይችል ነበር ይላሉ?
በነገራችን ላይ አቶ መለስ ወደፊት ገፍቶ የሻዕቢያን ሠራዊት ማንበርከክና መደምሰስ አይቻልም የሚል ሃሳብ ነው ያቀረቡት፡፡ ኋላ ላይ የመጡ መረጃዎች ግን ማንበርከክ ይቻል እንደነበርና… ያለቀለት ጉዳይ እንደነበረ ይጠቁማሉ የኤርትራ ባለስልጣናትም እየተናገሩት ነው። ለምሣሌ ሃይልይሮ የተባለውና አሁን በእስር ላይ የሚገኘው፤ ባለስልጣን፤ “በቃ ወያኔ አጥለቅልቆናል፤ በሚገባ አሸንፎናል” ብሎ ነበር፡፡ ሌላ አድሃኖም የሚባል የእነሱ አመራር፣ የሻዕቢያ ሠራዊት ከአሰብ ወደ ምጽዋ ማፈግፈግ ጀምሮ እንደነበር ጠቅሶ ከአስመራም ለማፈግፈግ ተቃርቦ ነበር ብሏል፡፡ ገፍተን ብንሄድ ኖሮ አሁን በአካባቢው የተፈጠረው ትርምስ ባልኖረ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ለ14 አመት ችግር ውስጥ ነው የከተታት የጉዳዩ እልባት አለማግኘት ነው፡፡ ሁሌም በተጠንቀቅ እንድትቆም ነው ያደረጋት፡፡ ከዚያም በላይ ሻዕቢያ የሚደግፋቸው ሃይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ትርምስ ለመፍጠር ሲሞክሩ እያስተዋልን ነው፡፡ ሻዕቢያን ማስወገድ ቢቻል ኖሮ ለኤርትራ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ በጐ ነገር በተፈጠረ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ረጅም እፎይታ ያገኝ ነበር፡፡
አሁን እርስዎ የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው?
እኔ በአጠቃላይ እውነተኛውን፣ መሠረቱን ሊብራል ያደረገ ዲሞክራሲን መከተል በሚለው ነው የማምነው። ሊበራል ውስጥ ብዙ አይነት ክፍሎች አሉ፡፡ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ሶሻሊዝም ማርክሲዝምን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ማርክሲዝም ረሃብና ጭቆናን ለማስወገድ ጠቃሚ ነው፡፡ በደርግም በንጉሡ ስርአትም አሁንም ዲሞክራሲ በተግባር ስራ ላይ አልዋለም፡ ባለንበት እየረገጥን ነው፡፡ ዲሞክራሲ ያለ ነፃ የሲቪል ማህበረሰብ፣ ያለ ነፃ ፕሬስ አይታሰብም፡፡ ህብረተሰቡ በነፃነት ሣይንቀሳቀስ በየ5 አመቱ ምርጫ ማካሄድ ዲሞክራሲ አይደለም፡፡ መድብለ ፓርቲ በሌለበት ዲሞክራሲ የለም፡፡ በኢትዮጵያ እነዚህ ነገሮች እንኳ ብንተገብር ለውጥ ይመጣ ነበር፡፡ መጀመሪያ የዲሞክራሲ መሠረትን መገንባት ነበር የሚያስፈልገው፤ ከዚያ በኋላ ማርክሲስቱም፣ ሊበራሉም፣ ሌላውም የፈለገውን ሃሳብ ማራመድ ይችላል፡፡ እኔ አሁንም የፀና እምነቴ እውነተኛውን ዲሞክራሲ መተግበር በሚለው ስለሆነ የምታገለውም ለዚሁ ነው፡፡
ከ1993 የህወኃት ክፍፍል በኋላ ከድርጅቱ የወጣችሁ ፖለቲከኞች አንድ ላይ መሠባሰብ አልቻላችሁም፤ ሁላችሁም በየፊናችሁ ነው የተበታተናችሁት? አንዳንድ ወገኖች ከድርጅቱ የወጣችሁትግለሰብ ላይ ባላችሁ ጥላቻ እንደሆነ ይናገራሉ…
እኛ አቶ መለስን የተቃወምነው በሉአላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያ ጋር በተያያዘም በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የተቃኘው ዲሞክራሲ ትክክል አይደለም የሚል ነበር። መለስም አቸንፌያለሁ ብሎ አንዳንዱን እስር ቤት ወርውሮታል፣ አንዳንዱን የቁም እስረኛ አድርጐታል፤ አንዳንዱን እንደገና ጫና ፈጥሮ እንዲመለስ አድርጐታል። ህወሐት የወጣን ሰዎች የጋራ ፕሮግራም አልነበረንም። በሁለቱ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ነበረን እንጂ የጋራ ፕሮግራም አልነበረንም፡፡ መታወቅ ያለበት ግን አቋም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እኛ ህይወት የሚያስከፍል አቋም ነው ወሰድነው፡፡
ከክፍሉ በኋላ አቶ መለስ አለማቀፍ ሰብዕና ያላቸው ሰው ሆነዋል፣ “የምጡቅ አስተሳሰብ ባለቤት” እየተባሉ ተሞካሽተዋል፡፡ በተቃራኒው የእናንተ ቡድን ደግሞ “ራሱን አላደሰም” ተብሎ ይወቀሳል፡፡ አስተሳሰባችሁን አንጥራችሁ ማውጣት አልቻላችሁም ተብላችሁ ትወቀሳላችሁ…
እኔና በአረና ፓርቲ ውስጥ ያለን ግለሰቦች መሰረታዊ ለውጥ አድርገናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ፕሮግራማችንን ማየት ይቻላል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምናምን የሚል ማጭበርበር የሌለበት ፕሮግራም እንዲነደፍ አድርገናል። በባህር በር ጉዳይም ኢትዮጵያ የባህር በር ይገባታል ብለናል፣ መሬት የመንግስት መሆን የለበትም፣ የህዝብ ነው የሚል አቋም ወስደናል፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያም መሰረታዊ አቋም በመውሰድ መገንጠል የሚባል ነገር መኖር የለበትም ብለናል፡፡ ኢህአዴግ ግን ባለበት አቋሙ ነው የፀናው፡፡ መለስ መች የአይዲኦሎጂ ለውጥ አመጣ? የተለየ አይዲኦሎጂ አምጥቶ ቢሆን ኖሮ እንደተባለው እኛ ባለንበት ቆመናል በሚል ተብለን ልንወቀስ እንችላለን፡፡ አንድ ነገር ግን ለውጥ መጥቷል፡፡ እኛ ስንቶቻቸው የነበሩ ነገሮችን አቶ መለስ በተግባር አውሎታል፡፡ የአለማቀፍ ድርጅቶችና ሃብታም ሃገሮችን ተላላኪነትን በስራ ላይ አውሎታል፡፡ መለስ ይኑርም አይኑርም ኢህአዴግ አለማቀፍ ተቀባይነት ያገኘው ወደ ሱማሌ ግባ ሲባል በመግባቱና የተላላኪነት ሚና በመወጣቱ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ሚና የሚወጣላቸውን አካል ደግሞ እነዚህ ሃገሮች ተክለ ሰውነቱን ይገነቡታል፡፡ ዲፕሎማሲ የጥቅም ጉዳይ ስለሆነ እነዚህ ሃገሮች የደገፋቸው ወይም የታዘዘላቸው መሪ ካገኙ ሰብዕናውን ይገነቡታል እንጂ አቶ መለስ ኢህአዴግ ይከተለው ከነበረው ርዕዮተ አለም የመጠቀ አስተሳሰብ ስለተከተለ አይመስለኝም፡፡
በመፅሀፉ ከትግሉ ጀምሮ እስከ ህወሐት ክፍፍል ድረስ ስህተት ያሏቸውን ጉዳዮች በግልፅ አስቀምጠዋል፤ እርስዎ እነዚያን ስህተቶች ተሸክመው እንዴት እስከ ክፍፍሉ ድረስ ዘለቁ? ለምን በወቅቱ እርምጃ አልወሰዱም?
በወቅቱ ድርጅቱ የሚገመግማቸው ስህተቶች ነበሩ። ይኖራሉም፡፡ ግን ሁልጊዜ በሂደት ይታረማሉ የሚል ሃሳብ ነበረኝ፡፡ መሰረታዊ ቢሆን እንኳ ተወያይተን የምናርማቸው ጉዳዮች ነው የሚሆኑት ብለን እናስብ ነበር፡፡ በክፍፍሉ ወቅት ግን እነዚያ ችግሮች መታረም አይችሉም ብለን አቋም ወሰድን፡፡ አንዳንድ ስህተቶች ደግሞ ከምንከተለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ነበር የሚመነጩት፡፡ ያን ያየሁት ከወጣን በኋላ ነው፡፡ ስንከፋፈል እንኳ ሁለታችንም የነበረን ርዕዮተ ዓለም አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ከወጡት አሁንም አብዮታዊ ዲሞክራሲን የሚከተሉ ይኖሩ ይሆናል፡፡ እኔ ማርክሲዝምን በማምንበት ጊዜ፣ ዲሞክራሲ ለወዳጅ እንጂ ለጠላት መሰጠት የለበትም የሚል አቋም ነበረኝ። ግን ዲሞክራሲ ለሁሉም ዜጋ እኩል መድረስ ያለበት መሆኑን አምኛለሁ፡፡
በትግል ህይወትዎ አሁን ሲያስቡት የሚያስቆጭዎ ወይም የሚፀፅትዎ ነገር አለ?
በመታገሌ ፈፅሞ አልቆጭም፡፡ በተለይ ለ17 ዓመታት ያደረግሁት ትግል ሌሎች አላማዎች ባይሳኩም በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን አፍኖ የቆየው፣ ዜጎችን በግፍ ይገድል የነበረ ስርአት በመወገዱ እንደ ትልቅ ገድል አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡
ያም ሆኖ አንዳንድ አቋሞቼ ይፀፅቱኛል፡፡ ለምሳሌ በኤርትራ ላይ በትግሉ ወቅት የወሰድነው አቋም ይፀፅተኛል፡፡ የኢትዮጵያን ጥቅም ሳናስከብር ቅኝ ግዛት ነው ብለን ኤርትራ ነፃ እንድትወጣ መወሰናችንና የዚያ ውሳኔ አካል መሆኔ ይፀፅተኛል፡፡ ኤርትራ ነፃ መውጣቷ በእርግጥ የግድ ነበር፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ ስለሆነች የሚባለው ትልቅ ስህተት ነበር፤ ይሄ እስካሁን ድረስ ይፀፅተኛል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም በመካከላችን የነበረውን ልዩነት ከጦርነቱ ቀድመን ማሳወቅ ነበረብን ወይ የሚለውም ያሳስበኛል። ከዚያ ውጪ ግን በአይዲኦሎጂ በተፈጠሩት ስህተቶች የጊዜውን ፋሽን ተከትሎ የሚለዋወጥ በመሆኑ አልፀፀትም፤ እታረማለሁ እንጂ፡፡ ከሁሉም የሚፀፅተኝ ኢትዮጵያን የባህር በር የነሳው ውሳኔ ነው፡፡ በጦርነቱም ወቅት በእንዝላልነት ያን ያህል ዋጋ መከፈል ሳያስፈልገው መከፈሉ ያሳዝነኛል፡፡ ቀደም ብሎ መደራጀት ቢቻል ኖሮ፣ ያሁሉ ሞትና መፈናቀል ባልተከሰተ ነበር፡፡
የሚያስደስትዎ ወሳኔስ?
ብዙ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ግን ለመታገል መወሰኔ ያስደስተኛል፤ ችግሩ ሳይቀጥል በአንፃራዊነት ነፃ ሆኜ መኖሬም ትልቁ የሚያስደስተኝ ነገር ነው፡፡ አሁን አገሪቱ ውስጥ መሰረታዊ ችግሮች አሉ፡- የሙስና ችግር ስር የሰደደ ነው፣ ብልሹ አሰራሮችና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች አሉ፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተበራክቷል፡፡ የ1997 ምርጫን ተከትሎ ከ190 በላይ ዜጎች ሲገደሉ የዚያ አካል አለመሆኔ ያስደስተኛል፡፡
ከአቶ መለስና ከአቶ ኃይለማርያም አመራር የትኛውን ይመርጣሉ?
በኢትዮጵያ ያለው ችግር የግለሰቦች አይደለም። በክፍፍሉ ከህውኃት የተለየነው ግለሰቦች መለስን አሸንፈን ስልጣን ብንይዝ ኖሮ እኛም አምባገነኖች እንሆን ነበር፡፡ ምናልባት በኤርትራና በሉአላዊነት ጉዳይ እንዲሁም በአንዳንድ ሃገራዊ ፖሊሲዎች ላይ የተሻለ ነገር የማምጣት እድል ሊኖረን ይችል ነበር፡፡ በተረፈ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስለምንቀጥል አምባገነን ከመሆን የሚያግደን የለም፡፡ ይሄን ርዕዮተ ዓለም ተከትሎ የሄደ ሰው አምባገነን ነው የሚሆነው፡፡ መሰረቱ እዚያ ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ነው ያለው፡፡ ርዕዮተ ዓለሙ ስልጣን አያከፋፍልም፣ በአንድ ሰው ላይ ነው የሚቆልለው፣ ተቃዋሚን አይፈቅድም፣ የሚቃወሙትን በጠላትነት ነው የሚያየው፡፡ ህዝቡ እንዳሻው እንዲንቀሳቀስ አይፈቅድም። ስለዚህ መለስም ይሁን ኃይለማርያም አምባገነን የሚያደርጋቸው የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡
ኤፈርት በማን ሃብት ነው የተቋቋመው?
በህወሐት ሃብት ነው የተቋቋመው፡፡
የህወሐት የሃብት ምንጭ ምን ነበር?
በዚያን ወቅት ጠላት ከሚለው ደርግና፣ ከውጭ እርዳታ ያገኘው ሃብት ነበር፡፡ በንግድ በኩልም የተለያዩ መርከቦች ነበሩት፤ ይነግድ ነበር፡፡ መነሻ የሆነው ከዚህ የተገኘው ሃብት ነው፡፡ እኔ መነሳት ያለበት የሚመስለኝ፣ ሃብቱ ህዝብን እየጠቀመ ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ ህዝቡስ ይሄን ሃብት መቆጣጠር ችሏል ወይ? የቦርዱ አባላትና ሊቀመንበሮች የፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ስሙ ነው ኢንዶውመንት እንጂ የህወሐት ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡
እንደ ሌላው ተቋም ብዙ ሃብት ቢይዝም ግልፅነትና ተጠያቂነት የለውም፡፡ ህዝቡ ወጪና ገቢውን አያውቅም፡፡ እንደ መርህ አንድ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። ኢንዶውመንት ማቋቋም ህጋዊ ነው፡፡ ፓርቲ ነጋዴ ሲሆንስ? ይሄ ጥያቄ ነው መነሳት ያለበት፡፡ በኤፈርት ዙሪያ የሙስና፣. የባለቤትነት ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ ምናልባት የሰጠው ጥቅም የምለው በሚከፈቱት ድርጅቶች ህዝቡ የስራ እድል ማግኘቱ ነው፡፡
የህወሐት 40ኛ ዓመት አከባበርን እንዴት አዩት?
ትግል መዘከር አለበት፡፡ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ለመጣል የተሰዉትን መዘከር አግባብነት አለው፤ አስፈላጊም ነው፡፡ እንኳን ለዚህ ትግል ህይወታቸውን ለሰጡት በግለሰብ ደረጃም ይዘከራል፡፡ ግን የሚከበርበት መንገድ አግባብ አይደለም፡፡ “ለምንድነው ለዚህ ፕሮግራም 10 ሚሊዮን ብር የሚወጣው?” የሚለው የግድ መነሳት አለበት፡፡
ህወሐት ከተመሰረተ 40 ዓመት፣ ስልጣን ከያዘ 23 ዓመት ሆኖታል፡፡ በአሉን ሲያከብሩ በነዚህ ዓመታት የተጓዙበትን አቅጣጫ መገምገም ነበረባቸው፡፡ ግን በተቃራኒው ህዝቡና ተቃዋሚዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመደፍጠጥና ህዝቡን ወደ ኋላ ለመመለስ ሞክረዋል፡፡
ህውሐት ራሱም ወደ ፊት እንዳያይ ነው ያደረጉት፡፡ ህዝቡንም “ያሁኑን አታንሳ፤ ደደቢትን ተመልከት፤ የከፈልነውን መስዋዕትነት አስብ” ህወሐት በዚህ መልኩ ህዝቡን በስሜት ወደ ኋላ ጎትቶ በአሉን ማክበሩ ስህተት ይመስለኛል፡፡  

መግቢያ
ኢሕአዴግ፣ የዐፄውን ሥርዐት ርዝራዥና የደርግን አስከፊ ሥርዐት አፈራርሼ አገሪቱን በተሻለ የዴሞክራሲ ጎዳና እየመራኹ ነው በማለት ያለመታከት እያበሠረና እየወተወተ ይገኛል። ካለፈው ሥርዐት አላቅቄኣችኋለኹ የሚለው የራሱ እውነታ ቢኖረውም፣ በአንጻሩ ግን ኢሕአዴግ ራሱ የሚያበጅልን ዐዲስ ቀንበር መልክ አውጥቶ ዐደባባይ ወጥቶ መታየቱ አልቀረም፡፡ ያረጀውን አገዛዝ በዐዲስ አሠራር ከሚጭንብን ከዚኽ ዐይነቱ ቀንበር መላቀቅ የኢሕአዴግ ችግር ሳይኾን፣ የእኛ የአገሪቱ ዜጎች ችግር እና የቤት ሥራ መኾኑን መረዳት ይኖርብናል።
የዚኽ መጣጥፍ ቀዳሚ ዓላማ÷ ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በላይ የቆየው የኢሕአዴግ አገዛዝ ከዴሞክራሲ፣ ከዜጎች ነጻነትና መብት አኳያ ምን ዐይነት መንገድ ይዞ እየኼደ እንደኾነና ኢሕአዴግ በጥቂቱም ቢኾን ከጀመረው የዴሞክራሲ መንገድ ስቶ የኋላ ኋላ ራሱን ወደ ኢ-ዴሞክራሲ አገዛዝ እንደምን እንደቀለበሰ በተወሰነ መልኩ ለማሳየት ነው። መጣጥፉ በሦስት ንኡሳን ርእሶች የተከፈለ ነው፡፡ በክፍል አንድ፣ የዴሞክራሲ እና የሊብራሊዝም ፅንሰ ሐሳቦችን ከአገራችን ኹኔታ ጋራ በማያያዝ የመንደርደሪያ ሐሳብ እሰጣለኹ። በክፍል ኹለት፣ በሰው ልጆች የቅርብ ታሪክ ውስጥ ዴሞክራሲ እና ነጻነት ለመጎናጸፍ ይበጃሉ የሚባሉት ተቋማት÷ ለምሳሌ፣ እንደ ፓርላማ፣ የፍትሕና የሚዲያ፣ የመድበለ ፓርቲና የምርጫ ሥርዐት እንዲኹም ሲቪል ማኅበራትን ኢሕአዴግ እንደምን መንፈሳቸውን ቀይሮ የራሱ የፖለቲካ መገልገያ እንዳደረጋቸው፤ የምርጫ ሥርዐቱን በምሳሌነት በማንሣት ሐተታና ትችቴን አቀርባለኹ። በክፍል ሦስት፣ በአገራችን የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የሚገኘውን አፍራሽ የኾነ የፍትሕ አቀራረብ በማሳየትና በመጨረሻም፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዐጭር ማስታወሻ በማኖር መጣጥፉን እቋጫለኹ።      
፩. የዴሞክራሲ እና የሊበራሊዝም ነገር
እንደ ዕውቁ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁር ሳሙኤል ፒ. ሃንቲንግተን እይታ፣ በቅርብ የሰው ልጅ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በተለያዩ ጊዜዎች ሦስት የዴሞክራሲ ሞገዶች ተከሥተዋል። ከፍጹማዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት የተደረጉትን ሽግግሮች ምሁሩ በሞገድ አምሳል ያቀርቧቸዋል። እንደእርሳቸው ትረካ፣ የመጀመሪያው ሞገድ ከፈረንሳይና ከአሜሪካ ዐብዮት በኋላ በ19ኛው ምእት መባቻ የተነሣው ሲኾን ተከታዩ ደግሞ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በብዙ አገሮች ውስጥ የታየው ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ ከ1974 እስከ 1990 (እ. አ. አ.) ሠላሳ ያኽል አገሮች ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት የተሸጋገሩበት ነው፤ ምሁሩ ይህን የሽግግር ወቅት “ሦስተኛው የዴሞክራሲ ሞገድ” የሚል ስያሜ ሰጥተውታል።
ከሦስተኛው ሞገድ በኋላ ግን ሒደቱ የዴሞክራሲ ልምላሜን እያጠወለገ፣ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ወደ ኋላ ይቀለበስ ጀምሯል፡፡ ከእኒኽ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንድዋ ናት። የአገሮቹ መንግሥታት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ግንባታ ገብተናል ብለው ሲያውጁ፣ ነጻነት እና የመብት ጥያቄዎች ቀዳሚ ቦታ ይይዛሉ ተብሎ ተገምቶ ነበር። ኾኖም ግን፣ እነዚህ መንግሥታት የዴሞክራሲን መዋቅር ሌጣውን ተቀበሉ እንጂ በባሕርያዊነት አብሮት የሚሔደውን የሊብራሊዝም ጎዳና ስላልተከተሉ፣ በአሉበት እየረገጡ ወደፊት መራመድ ተስኗቸዋል።
በዚህ ዙሪያ ወሳኝ ጥናቶችን ያደረጉ ሰዎች እንደሚናገሩት፣ የዴሞክራሲ እና የሊብራሊዝም ፖለቲካዊ መርሕ ከፍልስፍና አንጻር ሲታዩ አንድነትም ልዩነትም አላቸው። የሰው ልጅ ምሉዕ የኾነ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ፍትሐዊ ነጻነት ይኖረው ዘንድ የዴሞክራሲ እና የሊብራሊዝም መስተጋብር የግድ ይላል። ዴሞክራሲ የሚለው ቃል በዋናነት ሕዝብን ከዓምባገነናዊ ኀይል የሚከላከል ጋሻ (Demo-protection) ሲኾን፣ ሊብራሊዝም ደግሞ የሕዝብ ሉዓላዊነት (Demo-power) ነው። ዐዲሶቹ “ዴሞክራሲያዊ” መንግሥታት በተወሰነ ደረጃ የዴሞክራሲን አንዳንድ ፈለጎች ለመከተል ባይቸገሩም፣ የሊብራል ጥሪዎችን ማድመጥ ግን በእጅጉ ተስኗቸዋል።
ምናልባት፣ በዴሞክራሲ እና በሊብራሊዝም መሀል እንዴት ወይም ምን ዓይነት ልዩነት ሊኖር ይችላል ብለው የሚጠይቁ ሰዎች ስለሚኖሩ በዚኽ ዙሪያ ጥቂት ብለን ማለፉ ተገቢ ነው። አንደኛ፣ ዴሞክራሲ የሚያተኩረው በሥልጣን ክፍፍል፣ በየጊዜው በሚደረጉ ምርጫዎች፣ በብዙኃን መገናኛ፣ በመድበለ ፓርቲ፣ በሲቪል ማኅበራት… ወዘተ ተቋማዊ አያያዝና አሠራር ላይ ነው። በአንጻሩ ሊብራሊዝም በሕግ የበላይነት፣ በመሠረታዊ የሰው ልጆች ነጻነትና መብት ላይ ያተኩራል።
ኹለተኛ፣ ዴሞክራሲ የመንግሥት ሥልጣን በሚያዝበት መዋቅር ላይ ሲያተኩር፣ ሊብራሊዝም ደግሞ የሥልጣን ወንዝ ከገደቡ ወጥቶ ዜጎችን እንዳያጥለቀልቅ ለመከላከል፣ በምን መንገድ እየተቀየሰና እየተገራ መሔድ እንዳለበትና እንደሚገባው ይደነግጋል። ይኸውም ዴሞክራሲ ተሳትፎ ላይ ሲያተኩር ሊብራሊዝም ደግሞ ተጠያቂነት ላይ ያተኩራል። በአንዲት አገር መልካም የነጻነትና የፍትሕ ሕይወት መንገድ ተይዟል የሚባለው፣ ዴሞክራሲ የሚጠይቀው ሕዝባዊ ተሳትፎና ሊብራሊዝም የሚሻው መንግሥታዊ ተጠያቂነት በአንድነት ተባብረው ሲገኙ ነው።
በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ የዴሞክራሲ እና የሊበራሊዝም የአጽንዖት ልዩነት እንደተጠበቀ ኾኖ፣ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ኹኔታ ስንመጣ፣ ሥርዐቱ የኹለቱንም መሠረታዊ ጥሪዎች ማስተናገድ የተሣነው ኾኖ እናገኘዋለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከደርግ በኋላ፣ በተወሰነ መልኩ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ቢያገኝም፣ ሕገ መንግሥቱ እንደሚደነግገው የሥልጣን ባለቤትነትን አልተጎናጸፈም። ይህን ለማለት የሚያስደፍረው፣ የአገራችንን ፖለቲካ ከሕዝባዊ ተሳትፎና ከመንግሥታዊ ተጠያቂነት አንጻር ስንመለከተው ትልቅ ጉድለት በመኖሩ ነው፡፡
(፩) ሕዝባዊ ተሳትፎ፦ ዜጎች በሕይወታቸው፣ በንብረታቸው፣ በማኅበረሰባዊ ኹኔታዎቻቸው ወሳኝ በኾኑ ጉዳዮች ላይ የምክክርና የውሳኔዎች አካል ባልኾኑበት ሥርዐትና አሠራር ውስጥ የዴሞክራሲ መሠረታዊ ጥሪ የኾነው ሕዝባዊ ተሳትፎ አልተወለደም ማለት ነው። ለኢሕአዴግ ግን ተሳትፎ ማለት (ሀ)አስቀድሞ የወሰነውን ነገር ሥልጠና በሚል ፈሊጥ ወደ ሕዝብ ማውረድ፣ (ለ)ባለድርሻ በሚል ፈሊጥ የራሱን ወኪሎች መርጦ ውሳኔዎች በተሳትፎ የተገኙ ማስመሰል ነው። ለሐቀኛ ተሳትፎ ግን የንግግር ነጻነት እና የመሰብሰብ ነጻነት ያስፈልጋል። መንግሥት እና ዜጎች በእኩል ደረጃ መወያየታቸው ቀርቶ፣ መንግሥት አቀባይ ሕዝብ ደግሞ ተቀባይ ኾነዋል።  
(፪) ተጠያቂነት፦ መረጃ ከመንግሥት ወደ ሕዝብ የማይወርድበት አገር ውስጥ የተጠያቂነትን ሥርዐት ማሟላት በእጅጉ አስቸጋሪ ይኾናል። ሥርዐቱን ለማሟላት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የኾነ ሚዲያ ይኖር ዘንድ ግድ ይላል። ዜጎች መረጃ የሚያገኙበት መንገድ እስከሌላቸው ድረስ መንግሥትን ተጠያቂ ሊያደርጉባቸው የሚችሉባቸው መንገዶች ኹሉ ይዘጋሉ።
አንዳንድ የፖለቲካ ምሁራን፣ ዴሞክራሲ ለማበብ ረዘም ያለ ጊዜ ይጠይቃል፤ በመኾኑም ኢሕአዴግን የበለጸገ ዴሞክራሲ አላመጣም ብሎ መተቸት አግባብነት የለውም፤ የሚል መከላከያ ያቀርባሉ። የአፍሪቃ ዴሞክራሲ ገና ለጋ በመኾኑ ለመቶዎች ዓመታት ከቆየው ምዕራባዊ ዴሞክራሲ ጋራ ሊነጻጸር አይገባም፤ ሲሉም ይሞግታሉ። ለዚኽ ዓይነቱ አስተያየት ተገቢ መልስ ሰጥተዋል ብለን የምናምነው የ20ኛው ምእት ትልቁ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ጂዮቫኒ ሳርቶሪ (Giovanni Sartori) ናቸው። በእርሳቸው አመላለስ፣ ዴሞክራሲ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት መዋቅር እንጂ አንድ ወጥ ባለመኾኑ፣ አንድ መንግሥት ቢያንስ የዜጎችን የንግግር፣ የመሰብሰብና ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማክበር ምን ያኽል ጊዜ ያስፈልገዋል? ጋዜጠኛን ላለማሰር፣ የፖለቲካ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን ላለመከልከል ሥርዐቱ ስንት ዘመን መቆየት ይኖርበታል?    
በእኔ በኩል በዴሞክራሲ ፍላጎትና በገዢዎች ፍላጎት መሀል የተዘረጋው ቅራኔ እንደተጠበቀ ኾኖ፣ ከዚህ ቀደም ለማሳየት እንደሞከርኹት፣ የአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ ለችግር የተጋለጠበት አንዱ ምክንያት፣ አውሮጳውያን በዘመነ አብርሆ ለመቶ ዓመታት ያኽል እንደአደረጉት፣ በሊብራሊዝም ባህል ላይ የተመሠረተ የሐሳብና አመለካከትን የመግለጽ ነጻነት፣ የኅትመት ነጻነት፣ ሃይማኖታዊ መቻቻልና በጥቅሉ በመሠረታዊ የሰው ልጆች የነጻነት ጥያቄዎች ላይ አስቀድመን ብርቱ ሥራ ባለመሥራታችን ነው።
፪. ዐዲሶቹ የኢ-ዴሞክራሲያዊ ኀይሎች ሥርዐተ ተቋማት
በዚህ ርእስ ሥር በከፊል የማቀርበው ሐሳብ በዋናነት የተመረኮዘው፣ በቅርቡ የጀርመኑ የፖለቲካ ሳይንቲስት ፕሮፌሰር አንድሪያስ ሺድለር (Andreas Schedler) በ2009 (እ. አ. አ.) በዴሞክራሲ ስያሜ ስለሚንቀሳቀሱት ዐዲስ መንግሥታት በአጠኑት ጥናት ላይ ነው።
ቀደም ባለው ክፍል ለማሳየት እንደሞከርኹት፣ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ፒ. ሃንቲንግተን “ሦስተኛው የዴሞክራሲ ሞገድ” ወደፊት መገስገሡን ትቶ፣ የቀኝ-ኋላ ዙር መንገድ መከተሉን መግለጻቸውን አውስቻለኹ። ሌሎች ጸሐፍትም፣ ከዚኹ የገለጻ መንፈስ ጋራ በሚሔድ መልኩ፣ ይህን ፕሮፌሰሩ ‘ቅልበሳ’ ያሉትን ፅንሰ ሐሳብ፣ አንዴ ‘ኢ-ሊብራል ዴሞክራሲ’፣ አንዳንዴ ‘ኦተሪቴሪያን ዴሞክራሲ’ የሚሉ ስያሜዎች እየሰጡ ለመግለጽ ሞክረዋል። ፅንሰ ሐሳቡ በተለያዩ ስያሜዎች ቢገለጽም፣ በዋና ጭብጣቸው፣ የሥርዐቶቹን ‘ኢ-ዴሞክራሲያዊ’ ባሕርይ የሚያሳዩ መኾኑ ላይ ግን ሙሉ ስምምነትና አንድነት አላቸው።የዴሞክራሲ ሞገድ ውስጥ የተፈጠሩት ዐዲስ ሥርዓቶች፣ በውጣኔአቸው የነጻነትና የመብት ፍንጣቂ ቢታይባቸውም፣ ከሰብአዊ ነጻነት አኳያ ሲመዘኑ ግን የተመናመነ የተሰፋ መንገድ ላይ እንዳሉ መረዳት አዳጋች አይኾንም።
“ፍጹማዊ የሥልጣን አገዛዝ” ወይም ደግሞ “የጭቆና አገዛዝ” በሚል ቀደም ብሎ የሚታወቀው ስያሜ በዐዲሶቹ ሥርዐቶች ዐውድ ውስጥ “ዴሞክራሲያዊ” የሚል ቅጽል ተለጥፎለት እናገኘዋለን። እዚኽ ላይ ማንሣት የሚገባን መሠረታዊ ጥያቄ፣ “ዴሞክራሲያዊ” የሚለው ቃል ከእኒኽ ሥርዓቶች ስያሜ ጋራ ለምን አብሮ ተያይዞ ይቀርባል? የሚል መኾን ይኖርበታል። ይህን ጥያቄ የምናነሣበት ዋነኛ ምክንያት በቀደመው ዓምባገነናዊ አገዛዝ (Dictatorship) እና በዛሬው ጠቅላይ አገዛዝ (Authoritarianism) መካከል መሠረታዊ ዝምድናና ልዩነት ይኖር እንደኾን መፈተሽ ስላለብን ነው።
ፍተሻው በቀጥታ ወደ አገራችን ተጨባጭ ኹኔታ ያመጣናል። ለመኾኑ፣ በደርግ ሥርዐትና በኢሕአዴግ ሥርዐት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ደርግን “ዲክቴተርሺፕ”፣ ኢሕአዴግን ደግሞ “ኦተሪቴርያን” የምንላቸው ለምንድን ነው? የኹለቱ ሥርዐቶች ልዩነት ሲቀርብ፦ አንዱ ገዳይ፣ ጨፍጫፊ፣ አረመኔ ተደርጎ ይተነተናል፤ ሌላው ደግሞ፣ በወዳጆቹ ዘንድ፣ እንደ ነጻ አውጪ፣ የዴሞክራሲ አራማጅ ተደርጎ ሲቀርብ፣ በተቃዋሚዎቹ በኩል ደግሞ፣ እንደ ኢ-ዴሞክራሲያዊና ጎሰኛ ተደርገው እንደኾነ ዘወትር እንሰማለን። ኹለቱም አቀራረቦች ላይ ላዩን ሲታዩ በተወሰነ መልኩ እውነታ ቢኖራቸውም፣ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ግን፣ የኹለቱን ሥርዐቶች መሠረታዊ ልዩነት በበቂ አይነግሩንም። በመኾኑም የቀድሞውንና የዐዲሱን መንግሥታዊ ሥርዐቶች ልዩነት በምንመረምርበት ጊዜ፣ ፕሮፌሰር ሺድለር የሚያቀርቡት ሐሳብ የበለጠ ጠቃሚ ኾኖ እናገኘዋለን።
ቀዳሚ የሚኾነው የኹለቱም ሥርዐቶች ተልእኮ ሥልጣንን ማካበት እና ሥልጣን ላይ መቆየት ነው። ከዚኽ አንጻር፣ ኹለቱም ሥርዐቶች ግባቸው አንድ ነው፡፡ ከግቡ ለመድረስ የሚጠቀሙባቸው መንገዶች ግን የተለያዩ ናቸው። እንደ ፕሮፌሰር ሺድለር አቀራረብ፣ የቀድሞዎቹ ዓምባገነኖች ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚጠቀሙባቸው ተቋማት ወትሮውንም በታሪክ ውስጥ የሰውን ልጅ ነጻነት በመፈታተን የሚታወቁትን፣ እንደ ‘የጦር ኀይል’፣ ‘ፖሊስ’፣ ‘ጸጥታ’፣ ‘ደኅንነት’፣ ‘ሲቪል ታጣቂዎች’ ናቸው። በሌላ በኩል፣ ዐዲስ የመጡት ዴሞክራሲያዊ ነን የሚሉት ሥርዐቶች ደግሞ የድሮውን የመጨቆኛ ተቋማት ትተው፣ የሰውን ነጻነትና መብት ያስከብራሉ የሚባሉትን የፍትሕ፣ የሕግ አውጪ፣ የምርጫ፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋማትን ወዘተ… በጭቆና መሣሪያነት ይጠቀማሉ።
እዚህ ላይ ተገቢ የሚኾነው ጥያቄ፣ ለነጻነት የታሰቡ ተቋማት እንደምን ተቀልብሰው የመንግሥት መጠቀሚያ ለመኾን በቁ? የሚል ነው። በመኾኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ ገለጻ ከሰጠን በኋላ፣ የፍትሕ ተቋማትን፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋማትንና የምርጫ ተቋማትን በምሳሌነት እናነሣለን።
ከኹሉ አስቀድሞ፣ ዐዲሱ ሥርዐት ሥልጣን በሚይዝበት ጊዜ የሚረከበው “ባዶ የፖለቲካ ተቋማዊ መሬት” (institutional tabularasa) አያገኝም። እንዲያውም ካለፈው ሥርዐት የቀጠሉ ርዝራዥ ተቋማት ተፎካካሪ ሊኾኑበት ስለሚችሉ የሚጠቅመውን ተቋም ዐቅፎና አስቀጥሎ አይበጀኝም የሚለውን ያፈርሰዋል።
በኹለተኛ ደረጃ፣ ዴሞክራሲን ሊያራምዱ ይችላሉ የሚባሉትን ዐዲስ ተቋማት ይገነባል፤ ኾኖም ግን፣ ተቋማቱ በመጀመሪያ እንደ ሥርዐት የቆሙበትን መንፈስ ሽሮ ሕይወት አልባ በማድረግ ለታይታ፣ በቅርፃቸው ብቻ እውናዊ እንዲመስሉ ያደርጋቸዋል። በዚኽም ሳይገታ በራሱ ቁጥጥር ሥር ከአዋላቸው በኋላ፣ ተቋማቱን እንደ ለማዳ እንስሳ እዚያው ሥርዐቱ ግቢ ውስጥ ይለቃቅቸዋል፤ ነገር ግን እነኚኽ የተሽመደመዱና ለአገዛዙ የተገሩ ተቋማት እንዲኹ ተቀላቢ ኾነው አይቀመጡም። ሥርዐቱ እስከአለ ድረስ ትጉሃን የጭነት ፈረስ ኾነው አገልግሎታቸውን ያበረክታሉ።
በሦስተኛ ደረጃ፣ ሥርዐቱ ሲጀምር ሕገ መንግሥት ተቀርፆ በአንድ በኩል ከአሐዳዊ ወደ ፌደራላዊ ሥርዓት ሽግግር መደረጉ ተገልጧል፤ በሌላ በኩል ከአንድ ወጥ የሥልጣን ዘርፍ ወደተለያየ የሥልጣን ዘርፍ ሔዶ የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር በሕገ መንግሥቱ በሕግ ተደንግጓል፡፡ አሁን ምን ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለን በምንመለከትበት ጊዜ ግን የምናገኘው የሚከተለውን እውነታ ነው። ሕግ አስፈጻሚው ክፍል ወደ ጎን (Horizontal) እና ወደ ላይ (vertical) የሥልጣን ሽሚያ በማድረግ በአንድ በኩል ፌደራል ተቋሙ ላይ በሌላ በኩል የሕግ አውጪው እና የሕግ ተርጓሚው ላይ ትልቅ ጫና በማሳረፍ ሥልጣናቸውን በእጅጉ ገድቦታል። በመኾኑም፣ በእኒኽ ኹለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ፣ ሕግ አስፈጻሚው ተቋም ከሌሎቹ የመንግሥት ክፍሎች ኹሉ በበለጠ እየተጠናከረ እንዲኹም ሌሎቹን ተቋማት እያመነመነ ሔዷል።
ሀ) የፍትሕ ተቋማት፡-
በማንኛውም ሀገር ታሪክና በእኛም ነባራዊ ኹኔታ እንደምንረዳው፤ ያለሕግ ነጻነት የለም። እንዲኹም ሕግን ለመተግበር የፍትሕ ተቋማት ወሳኝ ድርሻ አላቸው። ኾኖም ግን የአንድን አገር ፍትሕ ለማስከበር የሕግ ተቋማት ራሳቸው በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የግድ ይላል። ይኸውም የራሳቸውን ልዕልና ያላስከበሩ ተቋማት የዜጎችን ነጻነት ያስከብራሉ ማለት ዘበት ስለኾነ ነው።
አንዳንድ ጸሐፍት እንደሚነግሩን፣ የጠቅላይነት ሥርዓቶች የፍትሕ ተቋማትን ልዕልናና አቋም ለመቦርቦርና ለማዳከም ሕጉን ለመጨቆኛ በሚኾን መልኩ ደጋግመው በማመቻቸት (Judicialization of repression) ሲተገብሩ ይስተዋላሉ። ይህን ለመተግበር ከሚከተሏቸው መንገዶች የተወሰኑትን እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።
የፍትሕ ተቋማትን ሥልጣን መገደብ (disempowerment)፤
የፍትሕ ተቋማትን መገደብ በምንልበት ጊዜ፤ የተለያየ እመቃ ደረጃ ያለው ነው። በመጀመሪያ፣ የተሠየሙትን ዳኞች ሥልጣን መገደብና ማሳነስ ነው፤ በተጨማሪም ለመመርመር የሚችሉበትን ወሰን በእጅጉ ማጣበብና በመጨረሻም ዳኞች ሊኖራቸው የሚገባውን የውሳኔ ነጻነት (ዲስግሬሽን) ማሳጠር ማለት ነው።
ለመንግሥት “ይበጃሉ” የሚባሉ ሰዎችን መሠየም፤ በዚህ ረድፍ የሚታየው ኢ-ፍትሐዊ ጉዞ የሚጀመረው በዳኝነት ወንበር ላይ የሚሠየሙት ዳኞች እየተመረጡ የሥርዐቱ ወዳጆች እንዲኾኑ መደረጉ ነው። የሕዝብ አስተዳደር ጥናት ያጠኑ አንዳንድ ምሁራን እንደሚነግሩን፤ አንደኛው የመንግሥት ችሎታ፣ ለጥቅማጥቅም ቀልባቸውን ሊሰጡ የሚችሉትን ነቅሶ የማውጣት ስልት ነው። እነኚኽም ለጥቅማጥቅምና ድጎማ የተመቻቹ ሹመኞች (incentive compatibility) ናቸው። በጥቅም የማይደለሉትን ደግሞ ቀጥተኛውን መንገድ ተከትለው እንዳይሔዱ በማስፈራራት ሐሳብን የማስፈጸም ጫና (dissuasive punishment) እንዲደርስባቸው ይደረጋል። ከዚኽም በተጨማሪ የፍትሕ ሒደቱን ረጅምና ውሳኔውን ለመሻር በሚያመች መልኩ ከታች ወደ ላይ እንዲሔድ፤ እልባቱ በረጅም የአቤቱታና የውሳኔ መሻርያ ሰንሰለት እንዲፈጸም ይደረጋል።
የተበታተነ የፍትሕ ሥርዐት፤
ሕጉን ለመጨቆኛ በሚኾን መልኩ ማመቻቸት (Judicialization of repression) በአንድ ሀገር ያለ የፍትሕ ሥርዓት አንድ ወጥ የኾነ ቅርጽ እንዳይኖረው፣ መደበኛ ከኾነው የሕግ ተቋም ተፎካካሪና በሕግ አስፈጻሚው ቁጥጥር ሥር የኾነ መንታ ተቋም በመፍጠር የመደበኛውን ፍርድ ቤት ተግባር ወደ ተቀጽላው ተቋም ማሸጋገር ነው።
ለ) የሚዲያ ቁጥጥር፤
ሚዲያን በሚመለከት ተቀዳሚው የኦተሪተርያን መንግሥታት ዓላማ፤ ፖለቲካዊ መረጃዎችን የማምረቻ ኃይልን መቆጣጠርና በአገሩ ውስጥ ብቸኛ አምራች ኾኖ መቅረብ ነው። ዜጎች በተለይ የፖለቲካ መረጃን በአማራጭ እንዳያገኙና ተፎካካሪ የኾነ የፖለቲካ ምልከታ እንዳይኖር ፍጹማዊ ሥልጣንን የተጎናጸፉ መንግሥታት ከሚያደርጓቸው ዕቀባዎች መካከል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።
የመገናኛ ምንጮች ብዝኃነት በመከልከሉ ዜጎች የመገናኛ አውታር ባለቤት የመኾን ዕድል የላቸውም። በመኾኑም በአገሪቱ የሚገኙት ሚዲያዎች በመንግሥት ሥር በመኾናቸው፤ የዝግጅቱን ይዘት ለመወሰን፣ ሕዝቡ ምን መስማት እንዳለበትና ምን መስማት እንደሌለበት በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ ይችላሉ። አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ለግለሰቦች በባለቤትነት የተሰጡ ቢኾንም የትኩረት አቅጣጫቸው ጠንከር ያሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በማንሣት ወይም ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በትኩረት በመዘገብ እንዲሠሩ ስለማይፈቅድ ብዙ ጊዜ በመዝናኛ፣ በስፖርታዊ ዘገባዎችና ይህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የታጠሩ ፕሮግራሞችን በማስተላለፍ እንዲጠመዱ ያደርጓቸዋል። ይህ ዐይነቱ የመገናኛና ሚዲያ የትኩረት አቅጣጫ ለሥርዐቱ ብዙም አስጊ ባለመኾኑ ከጫና ለመገላገል የሚጠቅም መላ ኾኖ ሲያገለግል ይስተዋላል።
ሐ. የምርጫ ሥርዓት፡-
ወደ ዴሞክራሲ ጎዳና ገብተዋል የሚባሉት አገሮች ተቀዳሚ ሥራ የሠሩት በምርጫ ተቋማት ላይ ነው። መንግሥታት በአገራቸው ሕዝብ ፊትም ኾነ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ፊት በፍትሐዊ ምርጫ ሥርዐትና ሒደት ውስጥ ማለፋቸው የቅቡልነት መሠረታዊ ጥያቄ ኾኗል። የምርጫ አስፈላጊነት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ላይ እንኳን የሕግ ዕውቅና አግኝቶ ወቅታዊ እና እውነተኛ ምርጫ ማካሔድ የአገሮች ተቀዳሚ ሓላፊነት እንደኾነ ተቀምጧል።
በኢትዮጵያም በሕገ መንግሥቱ፣ እንደ አንድ የዴሞክራሲ ሽግግር ሒደት ውስጥ እንዳለ አገር፣ በየአምስት ዓመቱ አገሪቱን ለማስተዳደር ተፎካካሪ ፓርቲዎች በብሔራዊ ምርጫ ለመንግሥት ሥልጣን የሚወዳደሩበት ሥርዐት ተደንግጓል። ከዚኽም በመነሣት፤ የመጪው ግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. ውድድር ብሔራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና የሕዝብ ተአማኒነት ባለው መልኩ እንዲካሔድ አቅጣጫ ተቀምጧል። የሕዝብ ተአማኒነት የሚለው እንደ መሥፈርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠ ስላልሆነ ለጊዜው እንተወውና፣ “ነጻ” እና “ፍትሐዊ” በሚሉት ስያሜዎች ላይ እናተኩር። ከኹሉ አስቀድሞ፣ ቃላት በመስጠትና ቃላቱን በመደጋገም ብቻ እውንና ተጨባጭ ማድረግ ይቻላል ወይ? በአኹኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ልትጎናጸፍ ትችላለች ወይ? ስለ ነጻና ፍትሕዊ ምርጫ በመጠኑ ከአብራራኹ በኋላ፣ የጥያቄዎቹን ምላሽ ለአንባቢ እተዋለኹ።  
“ነጻ” እና “ፍትሐዊ” የሚለው ቃል በመጀመሪያ ብቅ ያለው እ.ኤ.አ. በ1927 ዓ.ም. የአሜሪካን ካልቨን ኮሌጅ ልኡክ ኒኳራጓ ለምትባለው አገር “አሜሪካ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እንድታካሂድ ቃል እሰጣለኹ፤” የሚል ንግግር ሲያደርግ ቃሉ የመጀመሪያ ዕውቅናውን አግኝቷል። ቀጥሎም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ1956 ዓ.ም የቶጎ ላንድን የወደፊት ኹኔታ በሕዝበ ውሳኔ ለማረጋገጥ ባወጣው ሪፖርት ላይ ይኸው ቃል ተደግሟል። በሦስተኛ ደረጃ፤ በ1978 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔና ቁጥጥር የናሚቢያ ነጻነት፣ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ከተካሔደ በኋላ ምክር ቤቱ የሒደቱን ፍትሐዊነትና ነጻ አካሔድ ለዓለም ሲያበሥር ቃላቱ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ለማግኘት በቅተዋል።
ኹለቱ ስያሜዎች አብዛኛውን ጊዜ በአንድነት ቢጠቀሱም፤ ይዘታቸውንና ትርጉማቸውን በተናጠል ለማየት እሞክራለኹ፡፡
(ሀ) የምርጫ ነጻ ሒደት ሲባል፡-
ከኹሉ አስቀድሞ ነጻ የሚለው ቃል ዜጎች የማይሸራረፍ የመምረጥ መብት እንዳላቸው የሚጠቁም ነው። የዜጎችን በነጻ የመምረጥ መብት ለመተግበር የሚከተሉት ኹኔታዎች መመቻቸት አለባቸው።
የመሰብሰብ እና የመመካከር ነጻነት፣
ማኅበራትን የማቋቋም መብት፣
የመንቀሳቀስ መብት፣
የመናገር መብት፣
የፖለቲካ ድባቡ ከዘለፋ፣ ከማስፈራራትና ከመዋከብ የጸዳ መኾን ይኖርበታል።
(ለ) ፍትሐዊ ምርጫ ስንል ደግሞ፡-
ተአማኒ በኾነ የምርጫ ቦርድ ሥር የድምፅ ቆጠራው መካሔዱ፣
ከምርጫው በፊትም ኾነ በኋላ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አለመግባባት ሲከሠት ፍትሐዊ የግጭት መፍትሔ የሚሰጥ ተቋም መኖሩ፣
ኹሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ውድድር ውስጥ እንዲገቡ ያልተጨናነቀና እኩል ዕድል መስጠት፣
ኹሉንም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያስተናግድ እኩል የሚዲያ አቅርቦት ማመቻቸት፣
የውድድሩ ሜዳ ለኹሉም ፓርቲዎች የተስተካከለ እንዲኾን ማድረግ ሲቻል፣
በዋናነት የመንግሥትና የፓርቲ የምርጫ ወጪ የሚወጣበት ቋት ሲለይ ነው።
ከላይ የጠቀስናቸው አንዳንድ ነጥቦች እንደሚያሳዩት፣ ነጻና ፍትሓዊ ምርጫ የሚሟላው በአንድ ቀን የድምፅ መስጫ ኮሮጆ ውስጥ ካርድ በማስገባት ሳይኾን ሦስት የምርጫ ኺደትን ሲያካትት ነው። (ሀ) ከምርጫ በፊት ያለው የአገሪቱ የፖለቲካ ድባብና የመወዳደሪያው ሜዳ መስተካከል፤ (ለ) የምርጫው ቀን ውሎ እና ገለልተኛ አወዳዳሪ ተቋም፤ (ሐ) ከምርጫው ዕለት በኋላ በተወዳዳሪዎችና በድምፅ ሰጪዎች መካከል ጭቅጭቅ ቢነሣ ዳኝነትን የሚሰጥ ገለልተኛ ተቋም። ከላይ ላነሣነውም ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለማግኘት፣ አንባቢ፣ የጠቀስናቸውን መስፈርቶች ከአገራችን ነባራዊው ኹኔታ ጋራ በማነጻጸር የራሱን ፍርድ መስጠት ይችላል።  
(ይቀጥላል)

============================================================

 “ሁሉም የጋዜጣው ኮፒዎች አሉኝ”

በሙያዬ የፅንስና የማህፀን ሀኪም ነኝ፡፡ ለመፅሀፍና ለጋዜጣ ልዩ ፍቅር ስላለኝ ላለፉት በርካታ ዓመታት አያሌ መፅሀፍትን እንዲሁም ጋዜጦችን አንብቤአለሁ፡፡ ጋዜጣ ሳነብ አልመርጥም፡፡ በተለይ አዲስ አድማስን አንብቤ ለአዟሪው መልሼ አላውቅም፡፡ መጀመሪያውኑም አዲስ አድማስን ስገዛ ርዕስ እና የፊት ገፅ አልመለከትም፡፡ መግዛት ግዴታዬ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ ገና ብርቱካናማውን የጋዜጣውን ሎጐ ስመለከት የሆነ ደስ የሚል ነገር ይሰማኛል፡
አዲስ አድማስ ባለፉት 15 ዓመታት እጅግ በርካታ ቁም ነገሮችን፣ አስተማሪና አዝናኝ ጉዳዮችን ሲያስኮመኩመን ኖሯል፡፡ “የእኛ ሰው በአሜሪካ”፣ “እንጨዋወት”---የመሳሰሉት አምዶች አይረሱኝም፡፡ መስራቹን አቶ አሰፋ ጐሳዬን ነፍሱን በገነት ያኑራት እላለሁ፡፡ እሱ ካለፈም በኋላ የጋዜጣው ህልውና እንዲቀጥል ያደረጉትን ቤተሰቦቹን ማመስገን እወዳለሁ፡  ጋዜጣው ከመነሻው ጀምሮ ቢታይ፤ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ፣ ወደ ጋዜጣ አሳታሚነት ለሚገቡ፣ በጋዜጠኝነት በተለይ በህትመት ሚዲያ ላይ ትምህርት ለሚከታተሉ ሁሉ አይነተኛ ግብአት ነው ባይ ነኝ፡፡
የእኛም ማህበር (ኢሶግ) በጋዜጣው ላይ “ላንቺና ላንተ” የተሰኘ ቋሚ አምድ አለው፡ በዚህ ዓምድ በሚወጣ ፅሁፍ በርካቶችን ማስተማር ተችሏል፡፡ በአገራችን እንደ ልብ ጋዜጣ በማይገኝበትና እንደ ልብ መፃፍ በማይቻልበት ሁኔታ እንኳን አዲስ አድማስ ሁሉን ተቋቁሞ፣ ሁሉን እንዳመሉ ችሎ መረጃ ያቀብለናል፡፡ በውስጡ ደግሞ እንደ ገጣሚና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ እንደነ አብደላ ዕዝራ፣ እንደነ ኤፍሬም እንዳለ እና መሰል ሳተና ብዕረኞች አሉት፡፡ ቀድሞም በርካታ ብርቱ ብርቱ ፀሐፊዎች ነበሩ፡ ያን ጊዜም አሁንም ጋዜጣውን አነበዋለሁ፡፡ ወንዱ ልጄ ሶፍትዌር ኢንጂነር ቢሆንም የእኔው ዓመል ተጋብቶበት፣ ቅዳሜ ቅዳሜ አዲስ አድማስን ብብቱ ስር ሸጉጦ መምጣት ከጀመረ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኖታል፡፡ ታዲያ እሱ ገዛ ብዬ እኔ መግዛቴን አልተውም፡፡ በዚህ ምክንያት ከመጀመሪያው እትም አንስቶ  የአድማስ ኮፒ አለኝ፡፡
አዲስ አድማስ ጋዜጣን ተውሶ የማይመልስልኝ ጠላቴ ነው፡፡ ለስራ ብዙ ጊዜ ወደተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት ስሄድ፣ ደንበኛዬ ጋዜጦቹን በጥንቃቄ ያስቀምጥልኛል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ከአገር ስወጣ ዌብሳይቱ ላይ ማንበብ መቻሌ ያስደስተኛል፡፡ ብቻ… በአዲስ አድማስ ደስተኛ ነኝ፡፡ ከአዲስ አድማስ ቀጥሎ የማንበብ ጥሜን የሚያረካልኝ የነበረውና እንደ ሃምሌ ፀሐይ ብልጭ ብሎ የጠፋው “አዲስ ነገር” የተባለ ጋዜጣ ነበር፡፡ ጋዜጣውም ተዘጋ፤ አዘጋጆቹም ኮበለሉ፡፡
ለዚህ ነው ከላይ እንደ ልብ መናገርና መፃፍ በማይቻልባት ኢትዮጵያ፤ ትችቱንም፣ ትዝብቱንም፣ ወቅታዊ ትኩሳቶችንም አለዝቦ በማቅረብና ማህበረሰቡን በማስተማር ሲተጋ 15 አመት መጓዙ አድማስን ያስመሰግነዋል የምለው፡ አሁንም በርካታ 15 ዓመቶችን ያክብር፡ አዘጋጆቹንም ፀሐፊዎቹንም ኢትዮጵያንም ፈጣሪ ይባርክ፡፡
(ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ)

     በአብዛኛው ፓርቲዎች ለብቻቸው አየር ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ ከዜጎች ተጨባጭ ችግር ተነስተው መፍትሄ ለመፈለግ የመጡ አይደሉም፡፡ መሰረት የሌለው አመለካከታቸውን ዜጎች ላይ የሚጭኑ ናቸው፡፡ ለመመረጥ ብቻ ብሎ የፖለቲካ አስተሳሰብን ከህዝብ ቃርሞ መሄድ ትክክል አይደለም፡፡ እኔ ብመረጥ፤ በምን አገባኝ ስሜት መያዛችን፣ ምን ዋጋ አለው በሚል ተስፋ ቆራጭነት ቁጭ ማለታችን እንዲያበቃ የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት እፈልጋለሁ፡፡”
(ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሣ፤ ለፓርላማ የግል ዕጩ ተወዳዳሪ በነበሩ ወቅት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከሰጡት ቃለ - ምልልስ የተወሰደ፤
የካቲት 11 ቀን 1992 ዓ.ም)

“አዲስ አበባ መስተዳድር ካለ ቅድመ ዝግጅትና ካለ ውይይት ድንገት በነዋሪው ላይ የሚጭናቸው ህጎችና ሌሎች መሰናክሎች የንግድ እንቅስቃሴውን አዳክመዋል፡፡ መስተዳደሩ በሩን ለውይይት ዘግቶ ለእርምት እድል ነፍጓል፡፡
መስተዳደሩ ራሱን ከነዋሪው አርቋል፡፡ ለማገልገል ሳይሆን በነዋሪው ለመገልገል የፈለገ ይመስላል፡፡”
የቀድሞ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት (አቶ ክቡር ገና፤ ምክር ቤቱ ባዘጋጀው “ምረጥ አዲስ አበባ” ዘመቻ ላይ  ከተናገሩት የተወሰደ፡፡
አዲስ አድማስ የካቲት 4 ቀን 1992 ዓ.ም)

“ከረጅም አመታት በኋላ ከሚወደኝ የሀገሬ ህዝብ ጋር ለመቀላቀል በመቻሌ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ ከዚህ የሙዚቃ ትርኢት የሚገኘው ገቢም በድርቅ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ የሚውል ይሆናል፡፡
ልዩ ፍቅር ከሚያሳየኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ሆኜ በድርቅ ለተጎዱት ወገኖቼ መርጃ እንዲሆን ማናቸውንም የኪነ ጥበብ ሀብቴን ብሰጥ ለእኔ መታደል ነው፡፡ ዋስትናችንና ኃይላችን የኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር መሆኑን ከልብ አምናለሁ፡፡”
(አስቴር አወቀ፤ ጥር 27 ቀን 1992 ዓ.ም በአገሯ የመጀመሪያ ኮንሰርቷን ስታቀርብ
ለአዲስ አድማስ ከላከችው መልዕክት የተወሰደ)

“አሁን በስራ ላይ ያሉትን ህጎች የሚመለከቱ መሰረታዊ ጉዳዮች ውስጥ ሳንገባ የህጉ አፈፃፀም ሂደት እንዲቀላጠፍ በማድረጉ ስራ ላይ ብዙ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ግን አክስዮን ገበያውን ከማቋቋም ሊገቱን አይችሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም በንጉሰ ነገስቱ ዘመን የአክስዮን ገበያ ነበር፡፡ አሁን ያለው የንግድ ህግም ያኔ የነበረው ነው፡፡ በመሆኑም የአክሲዮን ገበያው ሂደት ሙሉ በሙሉ ህጋዊ ነው፡፡ ህጋዊ እስከሆነ ድረስ በመንግስት በኩል ይኖራል ብለን የምንጠብቀው ጣልቃ ገብነት የለም፡፡ መንግስት በአንዳንድ መልኩ የገበያውን ሂደት የሚያቀላጥፉ ሁኔታዎችን ቢያመቻች ደስ ይለናል፡፡ ይህንንም ያደርጋል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ከዚህ ውጪ ከመንግስት ጋር የሚያጋጨን ነገር የሚኖር አይመስለኝም፡፡”
(አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፤  የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የመጀመሪያ እትም ላይ ስለ አክስዮን ገበያ ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ከተናገሩት የተወሰደ)

Published in ዜና

“የኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለም፣ በባህሪው አምባገነናዊ ነው” - ተቃዋሚዎች
“የምዕራባውያን አጀንዳን ለማስፈፀም የሚተጉ ናቸው”- ኢህአዴግ

    ተቃዋሚዎች፤ ኢህአዴግ የሚከተለው ርዕዮተዓለም ለዲሞክራሲ ትኩረት ያልሰጠ የአምባገነን ስርአት ተሞክሮ ነው የሚል ትችት የሰነዘሩ ሲሆን ኢህአዴግ በበኩሉ፤ የሶሻል ዲሞክራሲና የሊበራል ተከታዮች የምዕራባውያን አጀንዳዎን ለማስፈፀም የሚተጉ ናቸው ሲል ተችቷል፡፡
ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ት/ቤት በተዘጋጀው የፓርቲዎች ክርክር ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚከተሏቸውን ርዕዮተ ዓለሞች በማብራራት ተከራክረዋል፡፡
ኢህአዴግን ወክለው የተከራከሩት አቶ አባይ ፀሐዬ፤ “ልማታዊ ዲሞክራሲ” ጃፓን፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያና የመሳሰሉ ሃገራት የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም እንደሆነና በኢትዮጵያ እንዴት እየተተገበረ እንዳለ አቶ አባይ ፀሐዬ አብራርተዋል፡፡
ለልማታዊ መንግስት ማሳያነት ጃፓንና ደቡብ ኮሪያን በምሳሌነት የጠቀሱት አቶ አባይ፤ ምዕራባውያን በኢንዱስትሪ ለመደርጀት ከ200 ዓመት በላይ ሲፈጅባቸው ጃፓን በልማታዊ መንግስት ርዕዮተ ዓለም ተመርታ በ50 ዓመት ውስጥ ስኬታማ ሆናለች፤ ኢህአዴግም በዚህ መንገድ ኢትዮጵያን በፍጥነት ማሳደግ ይቻላል የሚል እምነት አለው ብለዋል፡፡ በልማታዊ መንግስት ሃገርን በአጭር ጊዜ ማደስና ማሳደግ ይቻላል ያሉት ተከራካሪ፤ ከሊበራሊዝምና ከሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮቶች የሚለየው የመንግስት ሚና በኢኮኖሚው ወሳኝ ድርሻ አለው በሚለው እምነቱ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ልማታዊ መንግስት በዲሞክራሲ እጥረት እንደሚታማ የጠቆሙት አቶ አባይ፤ ከነኮሪያና ጃፓን ጋር ተመሳሳይ ባለመሆናችን ኢህአዴግ ርዕዮተ አለሙን ወደ ኢትዮጵያ ሲያመጣ ዲሞክራሲያዊና መድብለ ፓርቲ ስርአትን የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ ነው ብለዋል፡፡
 “ልማታዊ መንግስታት አምባገነን ናቸው ይባላል፤ በእርግጥስ ዲሞክራሲን ማስተናገድ ይቻላል ወይ? በምሳሌነት የሚጠቀሱ ሃገራትስ እነማን ናቸው?” የሚል ጥያቄ ከመድረክ መሪው የቀረበላቸው አቶ አባይ፤ “ይቻላል! ነፃ የሆኑ ዲሞክራቲክ ተቋማትን (ፍ/ቤቶች፣ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ….) በማቋቋም ዲሞክራሲን ከልማቱ እኩል ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ይቻላል” ብለዋል፡፡ “በኛ ሃገር ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እየተደረገ ነው፣ ከ60 በላይ ፓርቲ፣ የግል ፕሬሶች እና የህግ ዕውቅና አለ” ያሉት አቶ አባይ፤ የአፈፃፀሙ ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጋሩት ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የልማታዊ ዲሞክራሲ ተከራካሪው አቶ አባይ ከታዳሚው ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል “ርዕዮተ አለሙ ውሳኔዎች ተግባራዊ የሚደረጉት ህዝብ ምክረ ሃሳብ ተጠይቆ መስማማት ላይ ሲደረስ ነው ቢልም በቅርቡ ብዙ ውዝግብና የሰው ህይወት መጥፋት ያስከተለውን የአዲስ አበባና የፊኒፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን በግድ ይተገበራል ብለው ተናግረዋል፡፡ ይሄ ከምን የመነጨ ነው?” የሚለው ይገኝበታል፡፡ አቶ አባይም “ችግሩ ተፈጥሮ በነበረ ወቅት የመንግስት አካላት ከህዝቡ ጋር ባደረጉት ውይይት በፕላኑ ላይ ህዝቡ ጋ የነበረው የግንዛቤ ማነስ መወገዱንና የህዝብ ፍላጎትን ለመደፍጠጥ የሚጥሩ ጥቂት ግለሰቦች እቅዱን ማደናቀፍ እንደማይችሉ ተናገርኩ እንጂ በግድ ይተገበራል አላልኩም፣ አሁንም ህዝብ የማይደግፈው ከሆነ ሊቀር ይችላል” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“ሃገሪቱ በምግብ ራሷን ችላለች” በሚለው የኢህአዴግ መከራከሪያ ላይም ሃገሪቱ ራሷን ከቻለች በየዓመቱ ሚሊዮኖች እንደተደራቡ በዓለማቀፍ ተቋማት መገለፁ ከምን የመጣ ነው? በቂ ምርት አለ ከተባለ የት ነው የተደበቀው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው፤ “ሃገሪቱ በምግብ ዋስትና ራሷን መቻሏ አለማቀፍ ተቋማትም ያረጋገጡት ነው፣ ችግሩ የምርት ስርጭት አለመስተካከሉ ነው” ብለዋል፡፡
የ“ሊበራል” ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ተወካይ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ ሊብራሊዝም በዋናነት በግለሰቦች መብት ላይ የሚያተኩርና የመንግስትን በኢኮኖሚው ጣልቃ መግባት የሚቃወም መሆኑን አስረድተው፤ ፓርቲያቸው የመንግስት ሥልጣን ቢይዝ የሶሻል ዲሞክራሲን አንዳንድ እሴቶች መሰረት አድርጎ ሊብራሊዝምን እንደሚተገብር ገልጸዋል፡፡
“ጥቂት ከበርቴዎችና ሰፊ በድህነት ውስጥ ያለ ማህበረሰብ ባለበት ሀገር ለሃብታሞች ይወግናል የሚባለው ሊብራሊዝም እንዴት ነው የሰፊውን ድሃ ማህበረሰብ ጥቅም፣ የሚያስጠብቀው?” የሚል ጥያቄ ከመድረክ መሪው የቀረበላቸው ዶ/ር ጫኔ፤ ሊብራል ዲሞክራሲ እንደኛ ላለ ታዳጊ አገር አግባብ ያለው ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ጭምር መሆኑን ጠቁመው ርዕዮተ ዓለሙ የሚያቅፈው የህብረተሰብ ክፍል ባለፀጎችን ብቻ ሳይሆን የሶሻል ዲሞክራሲ እሴቶችን ታሳቢ በማድረግ ጡረተኞችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አቅመ ደካሞችንና ድሃውን ህብረተሰብ እጅግ በተገደበ አካሄድ መፍትሄ የሚያመጣበትን መንገድ መንግስት ያመቻቻል፤ ድጋፍ የሚደረግለት ህብረተሰብ ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ እንዲበቃ ያደርጋል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“ሊብራል ዲሞክራሲን ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት ከህብረተሰብ ማህበራዊ ሞራል ተፃራሪ የሆኑ ግብረ ሰዶምን የመሳሰሉ ድርጊቶችን የግለሰብ መብት ነው ብለው ያከብራሉ፤ እናንተስ ምን አሰባችሁ?” የሚል ጥያቄ ከታዳሚው የቀረበላቸው ተከራካሪው፤ “የሊብራል አስተሳሰብ የግለሰቦች መብትን አጥብቆ የሚያስከብር ቢሆንም ከማህበረሰብ ወግና ስርአት ተቃራኒ የሆኑ ተግባራትን ይቃወማል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሶሻል ዲሞክራሲን ከርዕዮተ ዓለሙ አጀማመር አንስቶ አሁን ያለበትን ደረጃ የሚያስቃኝ ትንታኔ የሰጡት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ በዋናነት ርዕዮተ አለሙ በሶሻሊዝምና በሊብራሊዝም መሃል ሆኖ ከባለፀጋዎች የሚሰበሰበው ግብር ለድሆች በድጎማ መልክ ይከፋፈል የሚል ሰብአዊነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተው፤ መድረክ በምርጫው ቢያሸንፍ ይህን ርዕዮተ ዓለም መሰረት አድርጎ አገሪቱን እንደሚያስተዳድር ጠቁመዋል፡፡
ከመድረክ መሪው ለፕ/ር በየነ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል “ብዙ ሃብታም በሌለበትና በርካታ ደሃ ባለበት ሃገር እንዴት ባለ አኳኋን ነው ሃብታምና ድሃን ለማመጣጠን የሚሰራው?” የሚል ጥያቄ የቀረበ ሲሆን ተከራካሪውም ከስርአቱ ጋር ተዛምዶም ሆነ በሌላ መንገድ ከፍተኛ ሃብት ማካበት በቻለው ክፍልና በተራው ዜጋ መካከል የአሁኑን ያህል ልዩነቱ ሊሰፋ እንደማይገባ ገልፀው፤ አቅም በፈቀደ መጠን የብዙዎች ኑሮ  ሊሻሻል ስለሚገባ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ማመጣጠን ያስፈልጋል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ክርክሮችን እንደሚያዘጋጅ ተገልጿል፡፡

Published in ዜና

“አዲስ አድማስ መስዋዕትነት የከፈለ ጋዜጣ ነው”
ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም
(የአለማቀፍ የህግ ባለሙያና ፖለቲከኛ)
     አዲስ አድማስ እንደሌሎቹ ጋዜጦች በፕሬሱ እንቅስቃሴ ውስጥ መስዋዕትነት የከፈለ፣ ለእውነትና ለሃቅ የታገለ ጋዜጣ አድርጌ ነው የማየው፡፡ እርግጥ እንደ ሌሎቹ የመዘጋት እድል አልገጠመውም፡፡ እንደሚታወቀው አሁን በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ ያዘጋጃቸው የነበሩ ጋዜጦች በሙሉ ተዘግተዋል፡፡
አዲስ አድማስ ጋዜጣም ምናልባት አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በቀጭን ክር እየተራመደ ዘልቋል ብዬ አስባለሁ፡፡
ለወደፊትም እንደሚዘልቅ ተስፋ አደርጋለሁ። እስካሁን ድረስ ለመዝለቁም የአዘጋጆቹ ጥበብና ብልህነት ነው እንጂ አፈና ሳይደርስበት ቀርቶ አይደለም፡፡
ለወደፊትም ቢሆን አሁን በያዘው ጥበበኛ አካሄድ ቢቀጥል መልካም ነው፤ ባልሆነ መንገድ ሄዶ መዘጋቱ ለሀገርም ጉዳት ነው፡፡
በተቻለ መጠን የሚዘጋበት ደረጃ እንዳይደርስ በጥንቃቄና በአስተዋይነት ቢጓዝ የበለጠ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይሄኛው ጥሩ መንገድ ይመስለኛል፡፡  


Published in ዜና