በሙያዬ የፅንስና የማህፀን ሀኪም ነኝ፡፡ ለመፅሀፍና ለጋዜጣ ልዩ ፍቅር ስላለኝ ላለፉት በርካታ ዓመታት አያሌ መፅሀፍትን እንዲሁም ጋዜጦችን አንብቤአለሁ፡፡ ጋዜጣ ሳነብ አልመርጥም፡፡ በተለይ አዲስ አድማስን አንብቤ ለአዟሪው መልሼ አላውቅም፡፡ መጀመሪያውኑም አዲስ አድማስን ስገዛ ርዕስ እና የፊት ገፅ አልመለከትም፡፡ መግዛት ግዴታዬ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ ገና ብርቱካናማውን የጋዜጣውን ሎጐ ስመለከት የሆነ ደስ የሚል ነገር ይሰማኛል፡
አዲስ አድማስ ባለፉት 15 ዓመታት እጅግ በርካታ ቁም ነገሮችን፣ አስተማሪና አዝናኝ ጉዳዮችን ሲያስኮመኩመን ኖሯል፡፡ “የእኛ ሰው በአሜሪካ”፣ “እንጨዋወት”---የመሳሰሉት አምዶች አይረሱኝም፡፡ መስራቹን አቶ አሰፋ ጐሳዬን ነፍሱን በገነት ያኑራት እላለሁ፡፡ እሱ ካለፈም በኋላ የጋዜጣው ህልውና እንዲቀጥል ያደረጉትን ቤተሰቦቹን ማመስገን እወዳለሁ፡  ጋዜጣው ከመነሻው ጀምሮ ቢታይ፤ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ፣ ወደ ጋዜጣ አሳታሚነት ለሚገቡ፣ በጋዜጠኝነት በተለይ በህትመት ሚዲያ ላይ ትምህርት ለሚከታተሉ ሁሉ አይነተኛ ግብአት ነው ባይ ነኝ፡፡
የእኛም ማህበር (ኢሶግ) በጋዜጣው ላይ “ላንቺና ላንተ” የተሰኘ ቋሚ አምድ አለው፡ በዚህ ዓምድ በሚወጣ ፅሁፍ በርካቶችን ማስተማር ተችሏል፡፡ በአገራችን እንደ ልብ ጋዜጣ በማይገኝበትና እንደ ልብ መፃፍ በማይቻልበት ሁኔታ እንኳን አዲስ አድማስ ሁሉን ተቋቁሞ፣ ሁሉን እንዳመሉ ችሎ መረጃ ያቀብለናል፡፡ በውስጡ ደግሞ እንደ ገጣሚና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ እንደነ አብደላ ዕዝራ፣ እንደነ ኤፍሬም እንዳለ እና መሰል ሳተና ብዕረኞች አሉት፡፡ ቀድሞም በርካታ ብርቱ ብርቱ ፀሐፊዎች ነበሩ፡ ያን ጊዜም አሁንም ጋዜጣውን አነበዋለሁ፡፡ ወንዱ ልጄ ሶፍትዌር ኢንጂነር ቢሆንም የእኔው ዓመል ተጋብቶበት፣ ቅዳሜ ቅዳሜ አዲስ አድማስን ብብቱ ስር ሸጉጦ መምጣት ከጀመረ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኖታል፡፡ ታዲያ እሱ ገዛ ብዬ እኔ መግዛቴን አልተውም፡፡ በዚህ ምክንያት ከመጀመሪያው እትም አንስቶ  የአድማስ ኮፒ አለኝ፡፡
አዲስ አድማስ ጋዜጣን ተውሶ የማይመልስልኝ ጠላቴ ነው፡፡ ለስራ ብዙ ጊዜ ወደተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት ስሄድ፣ ደንበኛዬ ጋዜጦቹን በጥንቃቄ ያስቀምጥልኛል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ከአገር ስወጣ ዌብሳይቱ ላይ ማንበብ መቻሌ ያስደስተኛል፡፡ ብቻ… በአዲስ አድማስ ደስተኛ ነኝ፡፡ ከአዲስ አድማስ ቀጥሎ የማንበብ ጥሜን የሚያረካልኝ የነበረውና እንደ ሃምሌ ፀሐይ ብልጭ ብሎ የጠፋው “አዲስ ነገር” የተባለ ጋዜጣ ነበር፡፡ ጋዜጣውም ተዘጋ፤ አዘጋጆቹም ኮበለሉ፡፡
ለዚህ ነው ከላይ እንደ ልብ መናገርና መፃፍ በማይቻልባት ኢትዮጵያ፤ ትችቱንም፣ ትዝብቱንም፣ ወቅታዊ ትኩሳቶችንም አለዝቦ በማቅረብና ማህበረሰቡን በማስተማር ሲተጋ 15 አመት መጓዙ አድማስን ያስመሰግነዋል የምለው፡ አሁንም በርካታ 15 ዓመቶችን ያክብር፡ አዘጋጆቹንም ፀሐፊዎቹንም ኢትዮጵያንም ፈጣሪ ይባርክ፡፡
(ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ)

Published in ዜና
Tuesday, 03 March 2015 14:38

አዲስ አድማስ

Published in የግጥም ጥግ

የ“ረቡኒ” እና “ኒሻን” ዳይሬክተሮች እኩል አሸንፈዋል

  • የዘሪቱ ከበደ ፊልም በ4 ዘርፎች አሸንፏል
  • ኮሜዲያን ፍልፍሉ ታዳሚውን ሲያሳቅቅ አምሽቷል

   ሁለተኛው የጉማ ፊልም ሽልማት ከፊልም ምዝገባው እስከ ማጣሪያው እንዲሁም የሽልማት ስነስርዓቱ ድረስ ብዙ ወራትን ፈጅቷል፡፡ 67 ፊልሞች ለውድድር ተመዝግበው 27 የታጩ ሲሆን ፊልሞቹን ለመዳኘት 102 ዳኞችና ተመልካቾች ተሳትፈውበታል፡፡ በ17 ዘርፎች ሲካሄድ የቆየው የጉማ ፊልም ሽልማት ውድድር ባለፈው ሰኞ አሸናፊዎቹን በመሸለም ተጠናቋል፡፡
አርፍዶ መጀመር ዘግይቶ መጨረስ
የሽልማቱ ስነ-ስርዓት በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ እንደሚካሄድ በመጥሪያው ካርዱ ላይ ተገልጿል፡፡ ፕሮግራሙ የተጀመረው ግን እንደተለመደው በጣም ዘግይቶ ነው፡፡ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እንኳ አልተጀመረም ነበር፡፡ ታዳሚው ትዕግስቱ መሟጠጡን በፉጨት፣ በጭብጨባና በጩኸት ሲገልፅ ቆይቶ፣ 1፡10 ላይ ምላሽ አገኘ፡፡ የማስታወቂያ ባለሙያው አርቲስት ሽመልስ በቀለ ወደ መድረኩ ብቅ ብሎ ፕሮግራሙ በሰዓቱ ባለመጀመሩ ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ መድረኩን መምራት ጀመረ፡፡ የመድረክ አጋፋሪው እሱ ነበር፡፡  
የዕለቱ የክብር እንግዳ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አማካሪና በአሁኑ ወቅት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የጽ/ቤት ኃላፊና የሚኒስትሩ ልዩ ተወካይ  አቶ አሰፋ ከሲቶ፤ የመክፈቺያ ንግግር አድርገዋል፡፡ የተለያዩ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች፣ በርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የውድድሩ ተሳታፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች አዳራሹን ሞልተውት ነበር፡፡
ከሚኒስትሩ ተወካይ ንግግር በኋላ ቀጥታ ወደ ሽልማት ስነ-ስርዓቱ የተገባ ሲሆን ብቸኛው  የህይወት ዘመን ተሸላሚ ከያኒው ደበበ እሸቱ ለሽልማት ወደ መድረክ ተጠራ፡፡ ታዳሚው በሙሉ ከመቀመጫው ተነስቶ በጭብጨባና በፉጨት ለአንጋፋው የጥበብ ሰው ያለውን አክብሮትና አድናቆት ገለፀ፡፡ አርቲስቱ መድረክ ላይ እንደወጣ በወርቀ ዘቦ ጥልፍ የተንቆጠቆጠ ካባ ተደረበለት፡፡ ከአገር ውስጥ እስከ ሌሎች አለማት የሰራቸው የኪነ ጥበብ ስራዎች ታወሱ፡፡ አሁንም የታዳሚው አድናቆት አልቀነሰም፡፡ ደበበ ከአርቲስት ብርሃኑ ሽብሩ እጅ ዋንጫ ከተሸለመ በኋላ አጠር ያለች አዝናኝ ንግግር አድርጓል፤ “ወደዚህ አዳራሽ ስገባ አንድ ጋዜጠኛ ይዞኝ ‘አሁን መድረክ ላይ የምታደርገው ንግግር ምንድን ነው?’ ብሎ ጠየቀኝ፡፡ #ምንም አልተዘጋጀሁም መድረኩ ላይ ከወጣሁ በኋላ ልቤና አዕምሮዬ ተመካክረው የወሰኑትን እናገራለሁ” ብዬው ነበር” በማለት ነው ንግግር የጀመረው፡፡ “ዛሬ ከምነግራችሁ በላይ ደስ ብሎኛል፤ ሰዎች ዳር ሆነው ይሄ ፊልም ጥሩ ነው፣ ይሄኛው መጥፎ ነው ሲሉ እሰማለሁ፤ ለእኔ ግን ፊልም መስራት መጀመሩ ነው ትልቁ ነገር” ብሏል፡፡
እያደገ ስለመጣው የፊልም ኢንዱስትሪ የተናገረው የእድሜ ዘመን ተሸላሚው፤ በአንድ ወቅት አርቲስት ንጋቷ ከልካይ አንድ እርግማን ተራግመው እንደነበር ሲገልጽ ሁሉም እርግማኑን ለመስማት ጆሮውን ከፈተ፡፡ “…አርቲስቷ በመሬት ጉዳይ ሙግት ጀምረው መረታት ሳይኖርባቸው ተረቱና ኢትዮጵያ ልጆችሽ ሁሉ አዝማሪ  ይሁኑ አሉ” ሲል አዳራሹ በሳቅ ተናጋ፡፡
“ታዲያ ስለ አርቲስቷ ህይወት ለማወቅ በአንድ ወቅት ኢንተርቪው ሳደርግ “እትዬ ንጋቷ እርግማንሽ ደረሰ ወይስ አልደረሰም?” ብዬ ጠየቅኋት፤ አርቲስቷም “እንዴት አልደረሰም፤ ደረሰ እንጂ የደጅ አዝማች ሰብስቤ ልጅ ኩኩ ሰብስቤ እንኳን ዘፋኝ ስትሆን” አለችኝ፤ ሲል ሌላ የሳቅ ሁካታ በአዳራሹ ነገሰ፡፡ ከዚያም አርቲስቱ ላለፉት 44 ዓመታት እንደ እህትም እንደ ጓደኛም እንደ ጠበቃም እንደ ሚስትም ሆና ከጎኑ ሳትለይ አራት ልጆችና ሰባት የልጅ ልጆች እንዲያይ ላደረገችው ውድ ባለቤቱ ምስጋና አቀረበ፡፡ “እግዜር የጥበብ ሙያን በላያችሁ ይዝራባችሁ” ሲልም መረቀ፡፡ “የህይወት ዘመን ተሸላሚ ሆኗል ይበቃዋል ብላችሁ ካሰባችሁ ሲያምራችሁ ይቅር፤ ገና ብዙ እሰራለሁ” በማለትም ንግግሩን አጠናቆ ከመድረክ ወርዷል፡፡
ሽልማቱ ግን ቀጠለ፡፡ በምርጥ የተማሪ አጭር ፊልም ዘርፍ “ሃጢያት የሌለበት” በተሰኘው ፊልም አቤል ዳዊት አሸናፊ ሲሆን በምርጥ ድምፅ በ “ኒሻን” ፊልም ከዴንማርክ የመጣችው ኦሪያላ ዊንተር አሸንፋ ዳይሬክተሩ ይድነቃቸው ሹመቴ ሽልማቱን ተቀብሎላታል፡፡ በምርጥ ሙዚቃ በ “ቀሚስ የለበስኩለት” ፊልም እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ አበጋዝ ክብረወርቅና ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ ያሸነፉ ሲሆን አበጋዝ ባይገኝም ሽልማቱን ዘሪቱ ተቀብላለች፡
በምርጥ ስኮር አሁንም በ “ቀሚስ የለበስኩለት” አበጋዝ ክብረወርቅ አሸንፎ ሽልማቱን ዘሪቱ ከበደ ከሙዚቃው ሃያሲው ሰርፀ - ፍሬ ስብሃት እጅ ተቀብላለታለች፡፡ በምርጥ የምስለ ገፅ ቅብ (ሜክአፕ) ዘርፍ “በጭስ ተደብቄ” ፊልም ዳዊት አለማየሁ አሸናፊ ሆኗል፡፡
በምርጥ ስክሪፕት የ “ረቡኒ” ፊልም ደራሲ ቅድስተ ይልማ ስታሸንፍ፣ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ ዘርፍ ደግሞ በ “ቀሚስ የለበስኩለት” ፊልም ታሪኩ ደስአለኝ አሸንፎ፣ ከእውቁ ፎቶግራፈር ታደሰ ደምሴ እጅ ዋንጫውን ተቀብሏል፡፡ ታሪኩ ከሽልማቱ በኋላ ባደረገው ንግግርም፤ “ይህ ዋንጫ መታሰቢያነቱ ዝዋይ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ ለሚገኘው ለብርቱው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ይሁንልኝ” ብሏል፡፡ ታዳሚውም በጭብጨባና በፉጨት አጅቦታል፡፡
በምርጥ ተስፋ የተጣለባት ተዋናይት ዘርፍ “በቀሚስ የለበስኩ’ለት” ፊልም ድምፃዊት ዘሪቱ  ከበደ አሸንፋ ዋንጫ የወሰደች ሲሆን ደጋግሞ ወደ መድረክ በመውጣትና በመውረድ ብዛት በምሽቱ የተወዳደራት አልተገኘም፡፡ ሽልማቱን ከወሰደች በኋላ የተሰማትን ስትናገርም፤ “ከተስፋ ጋር መሸለም ትልቅ ነገር ስለሆነ ደስታዬ ከፍተኛ ነው” ብላለች፡፡
በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ወንድ ተዋናይ በ“ያልታሰበው” ፊልም ህፃን ኢዮብ ዳዊት አሸናፊ ሆኗል፡፡ በምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይት ዘርፍ አሸናፊ የሆነችው እውቋ ተዋናይት አዚዛ አህመድ ስትሆን “በጭስ ተደብቄ” ፊልም ላይ ባሳየችው ብቃት ተሸልማለች፡፡ በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ “ኒሻን” ፊልም ላይ ብቃቱን ያሳየው አርቲስት አለባቸው መኮንን ያሸነፈ ሲሆን ከኮሜዲያን ደረጄ ሃይሌ እጅ ሽልማቱን ወስዷል፡፡ ደረጄ “ረዳት ለመሆን ምን አነሳሳህ?” ሲል ለተሸላሚው ያቀረበው ድንገተኛ ጥያቄ ታዳሚውን አስፈግጐታል፡፡
በምርጥ መሪ ሴት ተዋናይት “ረቡኒ” ፊልም ላይ የተመልካችን ቀልብ የማረከችው ሩታ መንግስተአብ አሸንፋ፣ ከአምናው የጉማ ፊልም ሽልማት ምርጥ ሴት መሪ ተዋናይት አሸናፊ ኤልሳቤት መላኩ እጅ ሽልማቷን ስትወስድ፣ በምርጥ ወንድ መሪ ተዋናይ “በጭስ ተደብቄ” ፊልም ላይ ተመልካችን ያስደመመው ዕውቁ አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ አሸናፊ ሆኖ ከአንጋፋው አርቲስት አብራር አብዶ እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡
በበደሌ ስፔሻል ምርጥ የተመልካች ምርጫ ፊልም “ረቡኒ” አሸናፊ ሲሆን ደራሲዋ ቅድስት ይልማ ከሄኒከን ማርኬቲንግ ማኔጀር ከወይዘሪት ሪታ ፀሐይ እጅ  ሽልማቷን ወስዳለች፡፡
በምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍ የ “ረቡኒ” ፊልም ዳይሬክተር ቅድስት ይልማ እና የ “ኒሻን” ዳይሬክተር ይድነቃቸው ሹመቴ የተመረጡ ሲሆን ሁለቱ ባለሙያዎች እንዴት እኩል አንደኛ ይወጣሉ የሚለው መነጋገሪያ ሆኖ አምሽቷል፡፡
በመጨረሻም በምርጥ ፊልም ዘርፍ “ኒሻን” አሸንፏል፡፡ ቀደም ብሎ በመድረኩ ላይ እንደተገለፀው፤ “ ኒሻን” በ11 ዘርፍ፣ “ረቡኒ” በ10 ዘርፍ፣ “ቀሚስ የለበስኩለት” በ10 ዘርፍ፣ “ያልታሰበው” በዘጠኝ ዘርፍ፣ “በጭስ ተደብቄ” በሰባት ዘርፍ፣ “400 ፍቅር” በአምስት ዘርፍ ታጭተው ነበር፡፡
በመቀጠል የተከናወነው በኪነ ጥበቡ ዘርፍ የረዥም ዘመን አገልግሎት ሰጥተው ያለፉ አንጋፋ አርቲስቶችን የማመስገንና የማስታወስ ፕሮግራም ሲሆን ከስድስት ወር በፊት ያለፉት የፊልም ባለሙያ ሚሼል ፓፓታኪስ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ሃይማኖት አለሙ፣ የመጀመሪያዋ ሴት ተዋናይት ሰላማዊት ገ/ሥላሴ፣ አርቲስት ሙናዬ መንበሩ፣ አርቲስት በላይነሽ አመዴ (ኩንዬ)፣ አብርሃም አስመላሽ፣ እንግዳዘር ነጋ፣ ዓለሙ ገ/አብ፣ ሲራክ ታደሰ እና አርቲስት ሙሉጌታ ባልቻ ፎቶአቸው በስክሪን እየታየ የታወሱ ሲሆን “በስራችሁ ህያው ናችሁ፤ እናመሰግናለን” ተብለዋል፡፡ በደሌ ቢራም ለእውቁ የኪነ ጥበብ ሰው ሚሼል ፓፓታኪስ መጠኑ ያልተገለፀ ገንዘብ በስጦታ አበርክቷል፡፡
ኮሜዲያን ፍልፍሉ ሲያሳቅቅ አመሸ
በሽልማት ሥነስርዓቱ ላይ የፕሮግራሙን ታዳሚዎች ለማዝናናት ሁለት ኮሜዲያን ተገኝተው ነበር፡፡ አንደኛው ኮሜዲያን የዓለም አቀፍ መሪዎችንና የአገራችንን ዕውቅ ሰዎች፣ ድምፅ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በማስመሰል ደረጃቸውን በጠበቁ ቀልዶቹ ሲያዝናና ያመሸ ሲሆን ኮሜዲያን በረከት በቀለ (ፍልፍሉ) ግን ህዝቡን ያስቃል ተብሎ ቢጠበቅም ሲያሳቅቅ አምሽቷል፡፡
ኮሜዲያኑ ምን እንደነካው ባይታወቅም ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት የራቀ፣ ፕሮግራሙን የታደሙትን ህፃናትና አዛውንት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ችኮ ቀልድ በማቅረብ ተመልካቹን አበሳጭቷል፡፡
አንድ የሽልማት ሥነስርዓቱን የታደሙ አዛውንት በሰጡት አስተያየት፤ “በአሁኑ ሰዓት የኮሜዲ ስራ የተከበረ ትልቅ ሙያ ቢሆንም እንደዚህ ዓይነት ቀልዶች ሙያውን እንዳያረክሱት እሰጋለሁ” ብለዋል፡፡  “የጉማ ፊልም ሽልማት አዘጋጆች፤ በፍልፍሉ ሲዘለፉና ሲቀለድባቸው ያመሹትን ታዳሚዎች በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው” ያሉት ደግሞ በእንግድነት ተጋብዘው የተገኙ አንድ  የግል ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡
ከተባለበት ሰዓት እጅጉን ዘግይቶ የተጀመረው የሽልማት ሥነስርዓት ፕሮግራሙ ከምሽቱ 4፡20 ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን አብዛኛው ታዳሚ (የትራንስፖርት እጥረትን በመፍራት) ከ3፡30 ጀምሮ አዳራሹን እየለቀቀ ወጥቷል፡፡

Published in ጥበብ

በሀገራችን ያለው የሙያ ማህበራት ቁጥር ከጊዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ እነዚህ የሙያ ማህበራት ከአባላቱ ባሻገር ለሙያ ዘርፉ ብሎም ለሀገር እድገት የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በህክምናው ዘርፍ ከተቋቋሙ የሙያ ማህበራት መካከል የኢትዮፕያ ፅንስና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር አንዱ ነው፡፡ ማህበሩ ባለፈው ሳምንት ሀያ ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ደረጃውን የጠበቀ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስልጠናን ማሳደግ በሚል መሪ ቃል በጅማ ዩንቨርሲቲ አካሂዷል፡፡
ዶክተር ደረጄ ንጉሴ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ናቸው። የዚህ አመት ጉባኤ ደረጃውን የጠበቀ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስልጠናን ማሳደግ የሚለው መሪ ቃል የተመረጠበትን ምክንያት ሲናገሩ፡-
“የዚህን አመት ጉባኤ ደረጃውን የጠበቀ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስልጠናን ማሳደግ በሚል አካሂደናል። ይህን መሪ ቃል የመረጥንበት ዋናው ምክንያት የያዝነው አመትየምእተ አመቱ     የልማትግቦች ማብቂያ እንደመሆኑ በጤናውም ዘርፍ እየተሰራ ያለውን ስራ ለማስቀጠል የባለሙያውን አቅም መገንባት አስፈላጊ ነው ብለን ስለምናምን ነው፡፡
የምእተአመቱ ግብ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚኖረው የጤና አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ደረጃቸውን     የጠበቁ ባለሙያዎች ማፍራት አስፈላጊ ስለሆነ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ምክክር ለማድረግ ይህን መሪ ቃል መርጠን የዚህን አመት ስብሰባ አካሂደናል ነው፡፡
ለሶስት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ላይ አስራ ሁለት ያህል ጥናታዊ ፀሁፎች የቀረቡ ሲሆን ፅሁፎቹ በተለያዩ የስነተዋልዶ ጤና ችግሮች እንዲሁም ከማህፀንና ፅንስ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በገራችን ያለውን ሁኔታ መሰረት በማድረግ የተሰሩ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ፅሁፎች ከቀረቡ በኋላም አባላቱና ለሌሎች የስብሰባው ተሳታፊዎች ተወያይተውበታል፡፡   
በጉባኤው ላይ የክብር እንግዳ ነበሩት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ዳይሪክተር የሆኑት ዶክተር ወንድምአገኝ እምቢ አለ፣፣ ‘’Ministry of  Health’s plans and issues in light of scaling up quality Obstetrics and Gynecology training’’ በሚል እርእስ ደረጃውን የጠበቀ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስልጠናን ለማሳደግ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል የተያዘውን እቅድ ለተሰብሳቢዎች አቅርበዋል፡፡
ማህበሩ ከጤና ጥበቃ ጋር በመተባበር በእናቶች ጤና ላይ በተለይ በእርግዝናና በወሊድ ግዜ የሚከሰትን የእናቶች ሞት ለመቀነስ በትብብር እየሰራ እንደሆነና እንዲህ አይነት የሙያ ማህበራት በጤናው ዘርፍ የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከማህበሩ ጋር ያለውን ግንኙነት ከምንግዜውም በላይ አጠንክሮ እንደሚሰራ ዶ/ር ወንድማገኝ ገልፀዋል። ከጽንስና ማህጠን ሐኪሞች ማህር ጋር ባለው የስራ ግንኙነትም የሚከተሰለውን ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ፅንስና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር ከተመሰረተበት ከፈረንጆቹ 1992/ አመተ ምህረት ጀምሮ የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እየሰራ ያለ ማህበር ነው፡፡ ከጤና ጥበቃም ጋር በመተባበር የሚሰራቸው የተለያዩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ በቅርቡም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በጤናው ዘርፍ ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለእናቶች ሞት ትልቅ ምክንያት የሆነውን የክህሎት ችግር ለመቅረፍ የድንገተኛ የፅንስ ህክምና ባለሙያዎችን እያሰለጠንን ነው፡፡ ይህን ስልጠና ከጀመርን አምስት አመት ቢሆንም በበቂ ሁኔታ እየተተገበረ አይደለም። ስለዚህ ይህን ስልጠና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ከእነዚህ ባለሙያዎች ጋር በትትብር እየሰራን ነው፡፡”



የያዝነው የፈረንጆቹ 2015 የምእተ አመቱ የልማት ግቦች ወይም millennium development goals ማብቂያ አመት እንደ መሆኑ በጤናው ዘርፍ እስከአሁን የታዩት እመርታዎች ምን ይመስላሉ ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር ወንድማገኝ ምላሽ ሲሰጡም፡-
የምእተ አመቱን የልማት ግቦችን በማሳካት እረገድ የጤናው ዘርፍ ትልቅ እመርታ አሳይቷል ማለት ያቻላል። የዛሬ ሁለት አመት የህፃናትን ሞት በመቀነስ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ተሰጥቷታል፡፡ የእናቶችን ሞት በተመለከተም ለውጡ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ለእናቶች ሞት ትልቁ ምክንያት የሆነው የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ የጤና አገልግሎቱ ተጠናክሮ እያንዳንዷ እናት አገልግሎቱን ፈላጊ እንድትሆንና በጤና ተቋም እንድትወልድ ማድረግ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እየተሰራ ያለ ስራ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከዛሬ አምስት አመት በፊት 6% የነበረው በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር አሁን ወደ 20% አድጓል፡፡ ስለዚህ በበቂ ሁኔታም ባይሆን የምእተ አመቱን ግብ ማሳካት ችለናል።” ብለዋል፡፡ በጉባኤው ከነበሩ ክንውኖች መካከል የደም ልገሳ ፕሮግራም አንዱ ነበር፡፡ የስብሰባው ተሳታፊዎች በበጎፈቃደኝነት ደም ለግሰዋል፡፡ የደም ልገሳ ፕሮግራሙ ባለሙያዎቹ ከህክምና ስራቸው በተጓዳኝ ለህብረተሱ አለኝታ መሆናቸውን ለማሳየት ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ ይገልፃሉ፡፡
“ይህ የደም ልገሳ ፕሮግራም የተዘጋጀው ባለሙያዎች ከህክምና ስራው ባሻግር ለህብረተሰቡ አለኝታ መሆናቸውን ለማሳየት ሲባል ነው፡፡ ህብረተሰቡም ይህንን በማየት የደምን አስፈላጊነት ተረድቶ ህይወትን ለማዳን ሲባል ደም መስጠት እንዳለበት ለማስተማር ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡”
ዶክተር ሙኸዲን አብዶ የማህፀንና ፅንስ ሀክምና እስፔሻሊስትና የማህበሩ የቦርድ አባል ናቸው፡፡ የህክምና ባለሙያዎች በእንዲህ አይነቱ የደም ልገሳ ፕሮችራሞች ላይ መሳተፋቸው ለሌላው የህብረተሰብ ክፍል የሚሰጠው የተለየ ትርጉም እንዳለ ይገልፃሉ?፡፡
“ባለሙያ እንደዚህ አይነት የደም ልገሳ ፕሮግራም ላይ መሳተፍ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ከእኛ ከባለሙያዎች የበለጠ የደም እጦት የሚያደርሰውን ጉዳት የሚያውቅ የለም፡፡ ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል የደም መፈሰስ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ስለዚህ በተለይ እንደኛ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ላይ ያሉ ባለሙያዎች በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ ደም መለገስ ከምንም በላይ አስደሳችና ሊዘወተር የሚገባው ነው፡፡”
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ባላካቸው ንጋቱም የዶክተር ሙኸዲንን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡“እንደሚታወቀው የማህፀንና ፅንስ ሀኪሞች በአብዛኛው ከደም ጋር የተያያዘ ስራ ላይ ነው ያለነው። እናቶች በተለያየ ምክንያት ደም ይፈሳቸዋል ለዚህም ከየደም ባንኩ ብዙ ደም እንጠይቃለን፡፡ የምንጠይቀውን ደም እራሳችንም በተወሰነ መልኩ አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለብን ሁልግዜም አስብ ነበር፡፡ ስለዚህ ዛሬ እድሉን አግኝቼ ደም በመስጠቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ከምንሰጠው የህክምና አገልግሎች በተጨማሪም ማህበራዊ ግዴታችን ነው ብዬ አስባለሁ ተምሳሌትነቱም ለማህበራችን አባላት ብቻ ሳይሆን ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡”


Published in ላንተና ላንቺ

የእርግዝናዬን ግዜ ሳስበው እጅግ ይዘገንነኛል፡፡ ልጄ አሁን ሁለተኛ አመቱን ይዞአል፡፡ በባለቤቴም በኩል ይሁን በእኔ በኩል ያሉ ቤተሰቦች አንድ ልጅ መደገም እንዳለበት     ሲነግሩኝ...በሁኔታው ባምንም ...ሳስበው ግን እጅግ ይመረኛል፡፡ ከክብደት ጀምሮ ገጽታዬ በሙሉ እንዲሁም የቆዳ ቀለሜ የእኔ አልነበረም፡፡ ጭራሽ ነበር የተበለሻሸሁት፡፡ እኔነቴ     ተመልሶ ይመጣል የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ አሁን ደግሞ ተመልሼ ባረግዝ ...ልክ አንደበፊቱ ልበላሽ ነው ብዬ በጣም እጨነቃለሁ፡፡ ለመሆኑ ሐኪሞቹ ምን ይላሉ?
ይህን ጥያቄ ያቀረበችው እናት በእድሜዋ ወደ ሀያ አምስት አመት ስትሆን የምትኖረውም በአዲስ አበባ ነው፡፡ ስሙዋ ደግሞ ቆንጂት ብርሀኔ ይባላል፡፡ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በእርግዝና ወቅት በእያንዳንዱ የእናቶች የሰውነት ክፍል የሚከሰቱ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ የሰውነት anatomic የምንለው ለውጥ ብቻ ሳይሆን በውስጣቸው የሚሰሩት ነገሮች በሙሉ የሚለወጡበት ሁኔታ ነው የሚኖረው፡፡ ይህም physiologic changes of pregnancy  ወይንም ከእርግዝናጋር በተያየዘ የሚከሰት ጤናማ የሆነ ለውጥ ማለት ነው፡፡ ይህ ለውጥ እንግዲህ በተለያዩ ሴቶች ላይ የሚኖረው ሁኔታ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሴቶች ላይ የማይቀር ለውጥ ነው፡፡ በእያንዳንዱ የሰውነታችን ስርአት ውስጥ የተለያዩ ለውጦች ይካሄዳሉ፡፡ በዚህ ወቅት የሚታዩት አካላዊ ለውጦች በዋናነት ከኪሎ መጨመር ጋር ተያይዘው የሚመጡ ለውጦች ናቸው፡፡  ክብደት ሲጨምር የትኞቹ ክፍሎች ናቸው የሚለወጡት ያልን እንደሆን ሰውነት ውስጥ ከሚከማቸው ፈሳሽ ጀምሮ የሚወፍሩ አካላት ይኖራሉ፡፡ ልጅ እና የእንግዴ ልጅ ሌላውን ክፍል ይይዛል፡፡ የማህፀን እድገት የራሱን የሆነ ክፍል ይይዛል፣ የሽርት ውሀ የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ሌሎች ሰውነት ውስጥ የሚከማቹ  ስብን ጨምሮ የሰውነት ቅርፅ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እነኚህ ለውጦች ከምን የተነሳ ነው የሚመጡት ብለን ያየን እንደሆነ በዋናነት በእርግዝና ወቅት የሚቀየሩት ወይንም የእናቶች ሰውነት ውስጥ የሚመነጨው የሆርሞን መጠን ነው፡፡ ይህ የሆርሞን መጠን መጀመሪያ እርግዝናው እንደተከሰተ የዘር ፍሬ ከሚመረትበት ወይንም እንቁላሏ ከወጣችበት ቦታ የሚቀረው ክፍል Corpus luteum  ከምንለው የሚወጣው ነው የመጀመሪያው የሆርሞን ለውጥ፡፡ በመቀጠልም የእንግዴ ልጅ የሚያመነጨው እጅግ በጣም ብዙ የሆነ የሆርሞን መጠን ይኖራል፡፡ እነኚህ ሆርሞኖች በእርግዝና ወቅት ለሚከሰቱ ለውጦች ወይንም physiologic changes of pregnancy
ለምንለው ምንጭ ናቸው፡፡ ሰውነት ውስጥ ፈሳሽ እንዲከማች፣ ስብ እንዲከማች፣ ልጅ እንዲያድግ የጠቀስኳቸው አካላት በሙሉ እድገት እንዲያሳዩ የሚያደርጉት እነኚህ ሆርሞኖች ናቸው፡፡ ስለዚህ የለውጡ ምንጭ ከእርግዝናው ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ከክብደት መጨመር በተጨማሪም ቆዳ ላይ የሚከሰቱ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ ፊት ላይ፣ በእናቶች ሆድ ላይ፣ በጡት ላይ፣ የቆዳ (መልክ) መቀየር አይነት ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ እና በተለያየ ቦታ በቆዳ ላይ የሚከሰቱ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ እነኚህ  በቆዳ ላይ የሚታዩት ለውጦችም ቢሆኑ ከሆርሞኖች የተነሳ የሚመጡ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ እናቶች በሁለቱም ጎናቸው ላይ የመጥቆር አይነት ሁኔታ ይኖራል፡፡ mealasma ወይንም colasma  ወይንም mask of pregnancy የሚሉት ነገር ነው፡፡ ይህም ኢስትሮጂን የሚባለው ሆርሞን ሰውነት ውስጥ ከመብዛቱ የተነሳ ቆዳ ላይ የሚከሰተው ለውጥ ነው ማለት ነው፡፡ የእናቶችን ሆድ ደግሞ ያየን እንደሆነ መሀል ላይ የመጥቆር ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይህም ከዛ ጋር የተያያዘ ነው  linea nigra  ነው የምንለው፡፡ ሌሎች ደግሞ ሸንተረሮች ይኖራሉ ሆድ፣ ጡት፣ እግር አካባቢ፣ እነኚህም ምንድነው በዋናነት የእነዚህ ሆርሞኖች መኖርና ሰውነት ክብደት እየጨመረ ሲሄድ ስብ እየተከማቸ ሲሄድ ወይንም ፈሳሽ እየተከማቸ ሲሄድ የመለጠጥና ከስር ያለው ቆዳ ወይም dermis የምንለው ቆዳ መሰነጣጠቅ ከዛም የመዳን ሁኔታዎች ናቸው እነኚህን ለውጦች የሚፈጥሩት ማለት ነው፡፡
አንዳንድ ግዜ ጤናማ ባልሆነ ሁኔታ ፈሳሽ ሰውነት ውስጥ የሚከማችበት ወይንም ከቆዳ ስር የሚከማችበት edema የምንለው ነገር ማለት ነው በብዛት የሚከማችበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ጤነኛ ባልሆነ ሁኔታ ብዙዎቹ እናቶች ከሰማኒያ % በላይ የሚሆኑት ላይ edema የምንለው ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ግን በጣም ከልክ ያለፈ አይደለም፡፡ ከልክ ያለፈ የሚሆነው ጤነኛ ባላሆነ ሁኔታ በአንዳንድ ከእርግዝና ጋር ሊመጡ በሚችሉ ችግሮች ለምሳሌ በደም ግፊት የተነሳ በጣም ብዙ ፈሳሽ ከቆዳ ስር ሊከማች ይችላል፣ ሆዳቸው ላይም ሊከማች ይችላል፣ እግራቸው ላይ ሊሆን ይችላል፣ እጃቸው ሊያብጥ ይችላል፣ ፊታቸው ሊያብጥ ይችላል፡፡ እነኚህ ጤነኛ ባልሆነ ሁኔታ የተከሰቱ ሁኔታዎች ናቸው ፡፡ ግን normally ጤነኛም ሆኖ የአንዱ ክብደት መጨመርና የሰውነት ቅርፅ መለዋወጥ ዋናው ምክንያት የዚህ የፈሳሽ መጠራቀምና የስብ ሰውነት ውስጥ መከማቸት ሁኔታዎች ናቸው፡፡ እንግዲህ እነኚህ ሰውነት ውስጥ ከእንግዴ ልጅ በብዛት በሚመነጩ ቅመሞች ወይንም ሆርሞኖች የተነሳ የሚከሰቱ ናቸው ማለት ነው፡፡
ጥ/ በእርግዝና ግዜ የሚወሰድ ቫይታሚን ለክብደት መጨመርና ለቆዳ መበለሻሸት ምክንያት ይሆናልን?
መ/ እንግዲህ በአጠቃላይ በእርግዝና ወቅት የእናቶችን አመጋገብ ወይንም የምግብ ሁኔታ ያየን እንደሆን በተመጣጠነ ሁኔታ እናቶች ምግብ ማግኘት አለባቸው፡፡ ምግብ ስንል በዋናነት macronutrient  እና micronutrient  ብለን ነው የምንከፍላቸው፡፡ macronutrient
በዋናነት የምንመገባቸው ለሰውነት ግንባታና ለሀይል የሚያገለግሉ ምግቦች ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ ካርቦሀይድሬት፣ ፋት እና ፕሮቲን እያልን የምንጠራቸው ዋናዎቹ ምግቦች ናቸው ማለት ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ  micronutrient  የምንላቸው ቫይታሚንና ሚንራሎች ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ናቸው፡፡ እነኚህ በዋናነት ጉልበት የመስጠትና ሰውነት መገንባት ቀጥተኛ የሆነ ተሳትፎ ባይኖራቸውም ሰውነት ውስጥ የሚካሄዱት የተለያዩ አይነት ሂደቶች በእነኚህ ሚንራሎችና ቫይታሚኖች በመታገዝ ነው፡፡ እነኚህ ለእናቲቱ ብቻ ሳይሆን እያደገ ላለው ፅንስ የሁለቱም የmacronutrient  እና  micronutrient  ምግቦች ምንጭ እናቲቱ ጋር ሲኖር ነው ወደ ልጁ ሊሄድ የሚችለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የተመጣጠነ ምግብ የሚመገቡ እናቶች እነኚህ አስፈላጊ የሆኑት ንጥረ ነገሮች ከምግብ ውስጥ በቀን የሚያስፈልገውን ያክል ያገኛሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ግን በቀን የሚያስፈልገውን ቫይታሚንና ፕሮቲን የምንላቸውን ንጥረ ነገሮች ከምግብ ውስጥ ብቻ የማይገኝባቸው ወይንም በቂ የማይሆኑበት ሁኔታዎች አሉ፡፡ አንዱ ምንድነው ምግባችን እነዛን ሚንራሎች ወይንም ቫይታሚኖች በበቂ ሁኔታ ያልያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢይዝም እንኳን በእርግዝና ወቅት የበለጠ  እነዚህን ቫይታሚንና ሚንራል አይረንና ፎሊክ የምንላቸው ነገሮች አስፈላጊ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ እነኚህ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች ናቸው እንጂ ከሚፈጠሩት የሰውነት ለውጦች ጋር በምንም መንገድ የማይገናኙ ናቸው፡፡ ቫይታሚኖቹና ሚንራሎቹ በእርግዝና ወቅት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ናቸው፡፡ አንዲት እናት በትክክል ማግኘት የሚገባት ንጥረነገር ነው፡፡
    በእርግዝና ወቅት ያለው የአመጋገብ ሁኔታን በተመለከተ አንዲት እናት እርጉዝ ካልሆነችው እናት የበለጠ ምግብ መመገብ አለባት፡፡ በእርግዝና ወቅት የሰውነቷ የካሎሪ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ይህ የሚሆነው ለምንድነው? አንዱ ለሰውነት ግንባታ ነው፣ ሁለተኛ ፅንሱ ጤናማ ሆኖ ለማደግ የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮች የሚገኙት ከእናቲቱ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ metabolic rate  የምንለው ነገር በእግዝና ወቅት ይጨምራል፡፡ ስለዚህ በእርግዝና ወቅት አንዲት እናት ቀድሞ ከምትመገበው የበለጠ መመገብ አለባት፡፡ የሰውነቷም ፍላጎት እያደገ ያለውም ፅንስ ይህንን ነው የሚፈልገው፡፡ ስለዚህ በምግብ ደረጃ ያየን እንደሆነ አንዲት እናት በእርግዝናዋ ወቅት ቢያንስ አንድ ተጨማሪ ምግብ መመገብ አለባት ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ይህ እንግዲህ ምንድነው አንዲት እናት በእርግዝናዋ ወቅት ወደ 300/ ኪሎ ካሎሪ ተጨማሪ ምግብ ትፈልጋለች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የምግብ ፍላጎት መጨመሩ የመጀመሪያዎቹን ሶስት ወራት ይሄ የማቅለሽለሹ፣ የማስመለሱና ምግብ የማስጠላቱ ነገር ከመኖሩ በስተቀር በተለይ ሁለተኛው ግማሽ የእርግዝና ወቅት እነኝህ ፍላጎቶች እየጨመሩ የሚሄዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይሄ ጤናማ የሆነው በእርግዝና ወቅት የሚኖረው የምግብም ሆነ የካሎሪ ወይንም የጉልበት መጠን ፍላጎት የሚጨምርበት ወቅት ነው ማለት ነው፡፡ ይህ በእርግዝና ወቅት ሲሆን የምታጠባ እናት ደግሞ የምትፈልገው የምግብ ወይንም የጉልበት ወይንም የካሎሪ መጠን ከእርጉዝ ሴት በተሻለ ነው፡፡ ይህም አንዲት የምታጠባ እናት ወደ 500/ ኪሎ ካሎሪ ተጨማሪ ምግብ የምትፈለፍግበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይህ በምግብ ሲሰላ ድሮ ከምትመገበው ሁለት ተጨማሪ ምግብ መመገብ አለባት፡፡ ስለዚህ ይሄ ለውጥ ከቫይታሚኖቹ የተነሳ አይደለም፡፡ በእርግጥ ቫይታሚኖች ሰውነታችን ውስጥ እያንዳንዱን metabolism የምንለውን ነገር የማመቻቸት ወይም facilitate የማድረግ ጠቀሜታ ነው ያላቸው፡፡
እያንዳንዱ ሰው የሚያመጣው ለውጥ ሊለያይ ይችላል፡፡ ግን በሰውነት ውስጥ የሚፈጠሩት ሆርሞኖች ለእነኚህ ልዩነቶች ወይም ለእነኚህ ለውጦች ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ለምን አንዳንድ እርጉዝ ሴቶች ይህን ቀለም ያዙ? ለምን ሌሎቹ ይህን አልያዙም? ለሚለው ይህ በተለያዩ ምክንያቶች ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ በአንፃራዊነት የእነኚህ ሆርሞኖች መጠን ምን ያክል ነው? በተጓዳኝ በእርግዝና ወቅት የሚመነጩ ሌሎች ነገሮች ይኖራሉ ወይ? አንዲት እናት ቆዳዋ ለፀሀይ ብርሀን ያለው sensitivity  ምን ያህል ነው? የሚሉት ነገሮች ይኖራሉ፡፡ melanosite  የምንላቸው ወይም የቆዳ ቀለምን ሊያመነጩ የሚችሉ ህዋሶች ምላሻቸው ምንድነው? ይህ በተለያዩ ምክንያቶች ሊለያይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ እንዳንድ እናቶች ፊታቸው ላይ የመጥቆር ሁኔታ ይኖራል አንዳንዶቹ ምንም አይነት ለውጥ አይኖራቸውም፡፡ በእርግዝና ብቻም ሳይሆን አንዳንድ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኒት የሚወስዱ እናቶች ፊታቸው ላይ የመጥቆር ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ፡፡ አንዳንዶቹ ላይ ምንም ላይፈጠር ይችላል፡፡ ይህ የሚያሳየው በዋናነት ሆርሞኖቹ ተፅእኖ ቢኖራቸውም ሆርሞኖቹ ብቻቸውን ሳይሆን ሌሎች ተጓዳኝ ወይም ያንን ነገር ሊገልፁ የሚችሉ ከ genetic ከመሳሰሉት environmental factors
ሊሆን ይችላል፡፡ የለውጦቹ ዋና ምንጮች ሆርሞኖቹ ቢሆኑም ለውጡ ግን እንደየ ሰዉ ሊለያይ ይችላል፡፡




Published in ላንተና ላንቺ

12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና  በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት  በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል፡፡ ሻምፒዮናውን በብቃት ለማካሄድ አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታድዬም በ5 ሚሊዮን ብር  ወጭ ሙሉ እድሳት ተደርጎለታል፡፡ እድሳቱ የስታዲየሙ አጥር፣ የመጸዳጃ ቤቶች ማስፋፋት፣ የመብራት፣ የተመልካቾች መቀመጫዎች፣ የትንሿን ስታዲየም የአስፓልት ንጣፍ፣ የፖውዛ መብራቶች ያካተተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናውን በማስተናገድ ወደፊት ትልልቅ ውድድሮችን የማዘጋጀት ፍላጎቷን ታነቃቃለች፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት በሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ እና 12 ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማንቀሳቀስ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ስታድዬም ሙሉ እድሳትና ለውድድሩ አጠቃላይ መስተንግዶ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ  ለበጀት እንደተመደበም ታውቋል፡፡
በሻምፒዮናው ላይ ለመሳተፍ  33 የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን አባል አገራት ማረጋገጫ ልከዋል፤ 618 የአፍሪካ ወጣት አትሌቶች በሜዳ እና በትራክ ላይ በሚካሄዱ 40 የስፖርት ውድድሮች ይሳተፋሉ፡፡ በመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ውድድሮች የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በተለይ የኢትዮጵያ እና የኬንያ በፍፁም የበላይነት ፉክክር እንደሚገቡ  ሲጠበቅ፤ የምእራብ አፍሪካ አገራት አትሌቶች በአጭር ርቀት ውድድሮች እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ በሜዳ ላይ ስፖርቶች ብልጫ እንደሚኖራቸው በመገለፅ ላይ ነው፡፡ በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ኢትዮጵያ 100፣ ናይጀሪያ 97 ፣ ሴራሊዮን 37፣ ሞሮኮ 35፣ ሱዳን 33፣ዚምባቡዌ 31፣ ካሜሮን 28፣ ቱኒዚያ 26፣ ቡርኪናፋሶ 23፣ ኮንጎ ብራዛቢል 19፣ ኡጋንዳ 19፣ ሴኔጋል 16፣ዛምቢያ 14፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ 13፣ ሩዋንዳ 7 ፣ ሲሼልስ 17፣አንጎላ 14  ፣ሶማሊያ 13፣ ኬንያ 12፣ ማሊ 11፣ ማዳጋስካር 8፣ አልጀሪያ 8፣ናምቢያ 8 ፣  ጋቦን 6 ግብፅ 6፣  ሌሴቶ 5፣፣ኮትዲቯር 5፣  ኬቬርዴ አይስላንድ 3፣ ፣ ስዋዚላንድ 3 እና  ጊኒ ቢሳው 1፣  ስፖርተኞችን አስመዝግበዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ሞሪሽዬስ፤ ባምቦስ በተባለች ከተማዋ ባስተናገደችው 11ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ29 አገራት የተውጣጡ 223 አትሌቶች በ40 የስፖርት ውድድሮች ተሳትፈው ነበር፡፡  15 አገራትአንድና ከዚያም በላይ ሜዳልያ በማግኘት የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተው 119  ሜዳልያዎችን ሰብስበዋል፡፡ ናይጄርያ በ19 ሜዳልያዎች (9 የወርቅ፤ 7 የብርና 3 የነሐስ) አንደኛ ደረጃ ነበራት፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ24 ሜዳልያዎች  (7 የወርቅ፤ 9 የብርና 8 የነሐስ) ሁለተኛ ደረጃ ስትወስድ 41 አትሌቶችን አሳትፋ የነበረችው ኢትዮጵያ በ22 ሜዳልያዎች (7 የወርቅ፤ 7 የብርና 8 የነሐስ) ሶስተኛ ደረጃ አግኝታ ነበር፡፡ ግብፅ በ11 ሜዳልያዎች (5 የወርቅ፤ 4 የብርና 2 የነሐስ)፤ ኬንያ በ17 ሜዳልያዎች፤(4 የወርቅ፤ 9 የብርና 4 የነሐስ) እንዲሁም ኡጋንዳ በ4 ሜዳልያዎች (2 የወርቅ፤ 1 የብርና 1 የነሐስ) እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ አከታትለው ወስደዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በ11ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው 7 የወርቅ ሜዳልያዎች 6 ስድስቱን ያስመዘገቡት ሴቶች ሲሆን በወንዶች የተገኘው 1 የወርቅ ሜዳልያ ብቻ ነበር፡፡ እነሱም በ800 ሜትር ወንዶች በረከት ካህሳይ አዳነ፤ በ800 ሜትር ሴቶች አለም ገብረእግዚአብሄር፤ በ1500 ሜትር ሴቶች ዳዊት ስዩም፤ በ3000 ሜትር ሴቶች ሃፍታምነሽ ተስፋዬ ሃይሉ፤ በ5000 ሜትር ሴቶች ሩቲ አጋ ሶራ፤ በ3ሺሜትር መሰናክል ወየንሸት አንሳ ወልደፃዲቅ እንዲሁም በ5000ሜትር የርምጃ ውድድር አስካለ ቲካሳ በንቲ ናቸው፡፡

በ2015 የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ቅድመ ማጣርያ ደደቢትና ቅዱስ ጊዮርጊስ   ዛሬ እና ነገ በባህርዳር ስታድዬም የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ከ2 ሳምንት በፊት የመጀመርያ ጨዋታቸውን ከሜዳ ውጭ ያደረጉት ሁለቱ ክለቦች ወደ 1ኛ  ዙር ማጣርያ ለመግባት  እድል አላቸው፡፡ 50 ሺህ ተመልካች የማስተናገድ አቅም ያለው የባህርዳር ስታድዬም   ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲያስተናግድ ከአፍሪካ እግር ኳስ  ኮንፌዴሬሽን እውቅና አግኝቷል፡፡ስታዲየሙ  የእግር ኳስ  ሜዳን ጨምሮ ሌሎች ሁለገብ ሩጫ፣ውርወራን፣ዝላይን ያካተተ የስፖርት ማዘውተሪያ እንዲኖረው ተደርጎ ተሰርቷል፡፡ 21 ሜትር ከፍታ ያለው ይህ ግዙፍ ስታዲየም በ2ኛ የግንባታ ምእራፉ 27ሄክታር ቦታ ላይ የሚያርፍ ግዙፍ የስፖርት መንደር  ይሰራለታል፡፡ አጠቃላይ ወጪው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች ከቅደመ ማጣርያ አንስቶ በ1ኛ እና በሁለተኛ ዙር ማጣርያዎች ውጤታማ በመሆን ወደ የምድብ ማጣርያዎች ለመግባት ከባድ ፈተና ገጥሟቸው ቆይቷል፡፡በተለይ በቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቻቸውን ማለፍ ከቻሉ በኋላ ወደ አንደኛ ዙር የማጣርያ ውድድር ሲሸጋገሩ ከሰሜን  እና ምዕራብ አፍሪካ ክለቦች በጥሎማለፍ ለደርሶ መልስ ጨዋታዎች እየተደለደሉ በዚህ ምእራፍ የሚገጥማቸውን ፉክክር ማለፍ ይከብዳቸዋል፡፡ ደደቢት በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ሲሳተፍ ዘንድሮ አራተኛው ነው፡፡
በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ብቸኛውን ተሳትፎ በ2014 እኤአ ላይ እንዲሁም ለሁለት ጊዜያት ደግሞ በ2011 እና በ2013 እኤአ ላይ በኮንፌደሬሽን ካፕ በመሳተፍ ውጤቱ በ1ኛው ዙር ማጣርያ ላይ በመሰናበት ተወስኖ ቆይቷል፡፡ አንጋፋው የኢትዮጵያ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ከ20 በላይ የውድድር ዘመናትን ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በአዲስ መዋቅር መካሄድ ጀምሮ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ዘንድሮ ሲሳተፍ 10ኛው ተሳትፎ ይሆናል፡፡ ባለፉት 9 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው ለ3 የውድድር ዘመናት ተሳትፎው በቅድመመማጣርያ ላይ ሲወሰን በ6 የውድድር ዘመናት እስከ 1ኛ ዙር ማጣርያ ብቻ ተጉዟል፡፡
በ8ኛው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ደደቢት ከሜዳው ውጭ የሲሸልሱን ኮት ዲ ኦርን በስታደ ደ አሚቴ 3ለ2 በሆነ ውጤት አሸንፎ ነበር፡፡ ዛሬ በባህርዳር በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ  በማንኛውም ውጤት አቻ መለያየት እና ማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፈዋል፡፡ ደደቢት በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የሚመራ ሲሆን የሲሸልሱን ክለብ ኮትዲኦር ባሻነፈበት ጨዋታ ሁለት ጎሎችን ዳዊት ፍቃዱ ከመረብ ሲያሳርፍ ናይጄሪያዊው 3ተኛውንና የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል፡፡  ዛሬ ደደቢት የሲሸልሱን ኮት ዲኦር ጥሎ ካለፈ ከቡርኪናፋሶው አርሲ ሮቦ ወይም ከናይጄርያው ዋሪ ዎልቭስ አሸናፊ ጋር በ1ኛ ዙር ማጣርያ የሚገናኝ ይሆናል፡፡በሁለቱ ክለቦች የቅድመ ማጣርያ  ጨዋታ የናይጄርያው ክለብ በሜዳው 1ለ0 እንዳሸነፈ ታውቋል፡፡
በ19ኛው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ በኤምሲ ኤል ኡልማ የተሸነፈው 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት ነበር፡፡ ነገ በባህርዳር በሚያደርገው የመልስ ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2 ንፁህ ጎሎች ካሸነፈ ወደ ቀጣዩ የአንደኛ ዙር ማጣርያ ያልፋል፡፡ በአንደኛ ዙር ማጣርያ ከጋናው አሻንቲ ኮቶኮ ጋር ሊገናኝ እንደሚችልም ታውቋል፡፡ የጋናው ክለብ በቅድመማጣርያው ከኢስት ላንድስ ጋር ተደልድሎ የነበረ ቢሆንም የሴራልዮኑ ክለብ ከውድድሩ በመውጣቱ በፎርፌ ሊያልፍ ችሏል፡፡
የፖርኩፒን ጦረኞች ተብሎ የሚጠራው የጋናው ክልብ አሻንቲ ኮቶኮ፤ ከተመሰረተ ከ82 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ አሻንቲ ኮቶኮ በጋና ፕሪሚዬር ሊግ ለ24 ጊዜያ ሻምፒዮን በመሆን የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን ያስመዘገበ ሲሆን ከአፍሪካ የኛው ክፍለዘመን ምርጥ ክለቦች አንዱ ሆኖ የተመዘገበ እንዲሁም በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ለሁለት ጊዚያት አሸናፊ በመሆን በውድድሩ  የከፍተኛ ውጤት ታሪክ በ7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ከ19 ወራት በኋላ በብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲጄኔሮ  በሚደረገው 31ኛው ኦሎምፒያድ  ኢትዮጵያ በብስክሌት 2  ኦሎምፒያን ፍቅረኛሞችን ታሳትፋለች፡፡ ከ1940ዎቹ መጨረሻ እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ ኢትዮጵያ በብስክሌት ስፖርት አምስት ኦሎምፒኮችን የተሳተፈች ሲሆን ሁለቱ ኦሎምፒያኖች ፅጋቡ ግርማይ እና ሃድነት አስመላሽ ለኢትዮጵያ በብስክሌት ስፖርት ስድስተኛው የኦሎምፒክ ተሳትፎ ማሳካት ችለዋል፡፡ ሁለቱ ኦሎምፒያኖች በኦሊምፒክ ለመካፈል የሚያበቃቸውን ሚኒማ ያስመዘገቡት  ከ2 ሳምንት በፊት ደቡብ አፍሪካ አስተናግዳ በነበረው የአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮና ላይ ነው፡፡ በኦሊምፒክ መድረክ ኢትዮጵያን ለመወከል የበቁት ሁለቱ የብስክሌት ኦሎምፒያኖች ፅጋቡ ገብረማርያምና ሐድነት አስመላሽ በትዳር ለመጣመር ከጫፍ የደረሱ ፍቅረኛሞች መሆናቸው ስኬታቸውን አስደናቂ አድርጎታል፡፡
ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ የሆነው ፅጋቡ ግርማይ፣ በስፖርቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፉክክር ደረጃ ያሳደገ እና የቀየረ የመጀመሪያው ብስክሌተኛ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ የጎዳና ላይ የብስክሌት ሻምፒዮና ላይ በመጀመርያው  በግሉ የወርቅ ሜዳልያ በመጎናፀፍ በአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያና ለምስራቅ አፍሪካ አስመዘገበ፡፡ ከዚህ ስኬቱ በኋላ ደግሞ በ48 ኪሎ ሜትር የነጠላ ውድድር  ርቀቱን 1 ሰዓት 03 ደቂቃ 05 ሰከንድ በማጠናቀቅ አምስተኛ ደረጃ ቢያገኝም ለኦሊምፒክ የሚያበቃውን ሚኒማ አሳክቷል፡፡  ስለሆነም ኢትዮጵያ በወንድ ብስክሌተኛ በኦሎምፒክ መድረክ ለመሳተፍ ስትበቃ ከ44 ዓመታት  በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የ23 ዓመቱ ፅጋቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የብስክሌት ሻምፒዮና ለሁለት ጊዜያት አሸንፏል፡፡ ፅጋቡ የፕሮፌሽናልነት ዕድል አግኝቶ የመጀመርያ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ክለብ ለመቀላቀል  ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመሄዱ በፊት የትራንስ ኢትዮጵያ ክለብ ተወዳዳሪ ነበር፡፡በፕሮፌሽናል ብስክሌተኛነት  ከ2012 እኤአ ጀምሮ ለሶስት ዓመታት በደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን ኩቤካ ስር ሲወዳደር ቆይቶ ላምፕሬ ሜሪዳ ለተባለ ክለብ ኮንትራት የፈረመው ከሁለት ወራት በፊት ነበር፡፡ አሁን አባል በሆነበት የጣሊያኑ የብስክሌት ክለብ ሳምፕሪ ሜሪዳ ፅጋቡ በዓመት እስከ 40,000 ዩሮ ክፍያ የሚፈፀምለት ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ ሆኗል፡፡ ከዓመት በፊት በቱር ዴ ታይዋን የጎዳና ላይ የብስክሌት ውድድር በማሸነፍ በዓለም አቀፍ ውድድር በኢትዮጵያ ብስክሌተኛ ለመጀመርያ ጊዜ የተመዘገበ ውጤት ሲያገኝ፤ በታላቁ የዓለማችን የብስክሌት ውድድር «ቱር ዴ ፍራንስ» ላይ በመሳተፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ ለመሆን ችሏል፡፡
በሴቶች ምድብም ደግሞ ሃድነት አስመላሽ የኦሎምፒክ ሚኒማ ያመጣችው 3ኛ ደረጃ ባገኘችበት የጎዳና ላይ የብስክሌት ሽቅድምድም ሲሆን ውጤቱ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሴት ብስክሌተኛ እንድትሳተፍ አድርጓል፡፡ ሃድነት  ተወልዳ ያደገችው በአክሱም ከተማ ሲሆን  የብስክሌት ስፖርትን ከጀመረች 10 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረችበት ወቅት ለሜታ አቦ ቢራ ክለብ ስትወዳደር ቆይታ ከዚያም ትራንስ ኢትዮጵያን ተቀላቅላለች፡፡ሐድነት አስመላሽ በስፖርት ሳይንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች፡፡ በብስክሌት ስፖርት የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ሴቶች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማድረግ የጀመሩት ባለፈው ዓመት ሲሆን በአገር ውስጥ በሚካሄዱ ውድድሮች ለተከታታይ ስምንት ዓመት የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የነበረችው ሃድነት አስመላሽ የኦሎምፒክ ተሳትፎን በማግኘቷ ከፍተኛ መነቃቃት ትፈጥራለች፡፡
በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ በኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያ በፈርቀዳጅነት ከተሳተፈችባቸው  ውድድሮች አንዱ የብስክሌት ስፖርት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከ60 ዓመታት በላይ እድሜ ላስቆጠረው የብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ የሚወክሏትን ሁለት ኦሎምፒያኖች ማግኘቷ ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡

12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና  በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት  በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል፡፡ ሻምፒዮናውን በብቃት ለማካሄድ አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታድዬም በ5 ሚሊዮን ብር  ወጭ ሙሉ እድሳት ተደርጎለታል፡፡ እድሳቱ የስታዲየሙ አጥር፣ የመጸዳጃ ቤቶች ማስፋፋት፣ የመብራት፣ የተመልካቾች መቀመጫዎች፣ የትንሿን ስታዲየም የአስፓልት ንጣፍ፣ የፖውዛ መብራቶች ያካተተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናውን በማስተናገድ ወደፊት ትልልቅ ውድድሮችን የማዘጋጀት ፍላጎቷን ታነቃቃለች፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት በሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ እና 12 ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማንቀሳቀስ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ስታድዬም ሙሉ እድሳትና ለውድድሩ አጠቃላይ መስተንግዶ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ  ለበጀት እንደተመደበም ታውቋል፡፡
በሻምፒዮናው ላይ ለመሳተፍ  33 የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን አባል አገራት ማረጋገጫ ልከዋል፤ 618 የአፍሪካ ወጣት አትሌቶች በሜዳ እና በትራክ ላይ በሚካሄዱ 40 የስፖርት ውድድሮች ይሳተፋሉ፡፡ በመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ውድድሮች የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በተለይ የኢትዮጵያ እና የኬንያ በፍፁም የበላይነት ፉክክር እንደሚገቡ  ሲጠበቅ፤ የምእራብ አፍሪካ አገራት አትሌቶች በአጭር ርቀት ውድድሮች እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ በሜዳ ላይ ስፖርቶች ብልጫ እንደሚኖራቸው በመገለፅ ላይ ነው፡፡ በ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ኢትዮጵያ 100፣ ናይጀሪያ 97 ፣ ሴራሊዮን 37፣ ሞሮኮ 35፣ ሱዳን 33፣ዚምባቡዌ 31፣ ካሜሮን 28፣ ቱኒዚያ 26፣ ቡርኪናፋሶ 23፣ ኮንጎ ብራዛቢል 19፣ ኡጋንዳ 19፣ ሴኔጋል 16፣ዛምቢያ 14፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ 13፣ ሩዋንዳ 7 ፣ ሲሼልስ 17፣አንጎላ 14  ፣ሶማሊያ 13፣ ኬንያ 12፣ ማሊ 11፣ ማዳጋስካር 8፣ አልጀሪያ 8፣ናምቢያ 8 ፣  ጋቦን 6 ግብፅ 6፣  ሌሴቶ 5፣፣ኮትዲቯር 5፣  ኬቬርዴ አይስላንድ 3፣ ፣ ስዋዚላንድ 3 እና  ጊኒ ቢሳው 1፣  ስፖርተኞችን አስመዝግበዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ሞሪሽዬስ፤ ባምቦስ በተባለች ከተማዋ ባስተናገደችው 11ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ29 አገራት የተውጣጡ 223 አትሌቶች በ40 የስፖርት ውድድሮች ተሳትፈው ነበር፡፡  15 አገራትአንድና ከዚያም በላይ ሜዳልያ በማግኘት የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተው 119  ሜዳልያዎችን ሰብስበዋል፡፡ ናይጄርያ በ19 ሜዳልያዎች (9 የወርቅ፤ 7 የብርና 3 የነሐስ) አንደኛ ደረጃ ነበራት፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ24 ሜዳልያዎች  (7 የወርቅ፤ 9 የብርና 8 የነሐስ) ሁለተኛ ደረጃ ስትወስድ 41 አትሌቶችን አሳትፋ የነበረችው ኢትዮጵያ በ22 ሜዳልያዎች (7 የወርቅ፤ 7 የብርና 8 የነሐስ) ሶስተኛ ደረጃ አግኝታ ነበር፡፡ ግብፅ በ11 ሜዳልያዎች (5 የወርቅ፤ 4 የብርና 2 የነሐስ)፤ ኬንያ በ17 ሜዳልያዎች፤(4 የወርቅ፤ 9 የብርና 4 የነሐስ) እንዲሁም ኡጋንዳ በ4 ሜዳልያዎች (2 የወርቅ፤ 1 የብርና 1 የነሐስ) እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ አከታትለው ወስደዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በ11ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው 7 የወርቅ ሜዳልያዎች 6 ስድስቱን ያስመዘገቡት ሴቶች ሲሆን በወንዶች የተገኘው 1 የወርቅ ሜዳልያ ብቻ ነበር፡፡ እነሱም በ800 ሜትር ወንዶች በረከት ካህሳይ አዳነ፤ በ800 ሜትር ሴቶች አለም ገብረእግዚአብሄር፤ በ1500 ሜትር ሴቶች ዳዊት ስዩም፤ በ3000 ሜትር ሴቶች ሃፍታምነሽ ተስፋዬ ሃይሉ፤ በ5000 ሜትር ሴቶች ሩቲ አጋ ሶራ፤ በ3ሺሜትር መሰናክል ወየንሸት አንሳ ወልደፃዲቅ እንዲሁም በ5000ሜትር የርምጃ ውድድር አስካለ ቲካሳ በንቲ ናቸው፡፡

እስላማዊ መንግስትን የማስፋፋት አላማ ይዞ የሚንቀሳቀሰው አይሲስ በቅርቡ በምዕራባውያን አገራት ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን አሰቃቂ ግድያዎች በሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ውስጥ ጭምብል አጥልቆ አሰቃቂ ግድያዎችን ሲፈጽም የሚታየውና ጂሃዲ ጆን በሚል ሃሰተኛ መጠሪያ የሚታወቀው ግለሰብ ትክክለኛ ማንነት መታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ግለሰቡ፣ ሞሃመድ ኢምዋዚ እንደሚባልና በትውልድ ኩዌታዊ፣ በዜግነት ደግሞ እንግሊዛዊ እንደሆነ ተረጋግጧል ያለው ዘገባው፣ ቀደም ሲል በእንግሊዝ የደህንነት አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡
 ግለሰቡ ባለፈው ነሐሴ ወር  በተለቀቀው የአይሲስ ቪዲዮ፣ አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ጄምስ ፎሌን አንገት  ሲቀላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደታየ ያስታወሰው ዘገባው፣ በማስከተልም አሜሪካውያንና እንግሊዛውያንን በጭካኔ ሲገድል መታየቱን አስታውቋል፡፡ በዚህ ወር መጀመሪያ በተለቀቀውና ጃፓናዊው ጋዜጠኛ ኬንጂ ጎቶ ሲገደል በሚያሳየው የአይሲስ ቪዲዮ ውስጥም፣ ይሄው ግለሰብ ግድያውን ሲፈጽም እንደታየ ዘገባው አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ የግድያ ተግባሩን ሲፈጽም ሙሉ ለሙሉ ጥቁር ልብስ ለብሶ፣ ፊቱን በጭንብል ጋርዶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ አንገት ከመቅላቱ በፊትም በእንግሊዛውያን የአነጋገር ቅላጼ ምዕራባውያን መንግስታትን ያወግዝ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
በአይሲስ ቁጥጥር ስር ቆይተው በቅርቡ የተለቀቁ የአይን እማኞች፣ ግለሰቡ በሶሪያ ከሚንቀሳቀሱ የቡድኑ እንግሊዛውያን ጂሃዲስት መሪዎች አንዱ እንደሆነ መመስከራቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡እስላማዊ መንግስትን የማስፋፋት አላማ ይዞ የሚንቀሳቀሰው አይሲስ በቅርቡ በምዕራባውያን አገራት ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን አሰቃቂ ግድያዎች በሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ውስጥ ጭምብል አጥልቆ አሰቃቂ ግድያዎችን ሲፈጽም የሚታየውና ጂሃዲ ጆን በሚል ሃሰተኛ መጠሪያ የሚታወቀው ግለሰብ ትክክለኛ ማንነት መታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ግለሰቡ፣ ሞሃመድ ኢምዋዚ እንደሚባልና በትውልድ ኩዌታዊ፣ በዜግነት ደግሞ እንግሊዛዊ እንደሆነ ተረጋግጧል ያለው ዘገባው፣ ቀደም ሲል በእንግሊዝ የደህንነት አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡
 ግለሰቡ ባለፈው ነሐሴ ወር  በተለቀቀው የአይሲስ ቪዲዮ፣ አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ጄምስ ፎሌን አንገት  ሲቀላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደታየ ያስታወሰው ዘገባው፣ በማስከተልም አሜሪካውያንና እንግሊዛውያንን በጭካኔ ሲገድል መታየቱን አስታውቋል፡፡ በዚህ ወር መጀመሪያ በተለቀቀውና ጃፓናዊው ጋዜጠኛ ኬንጂ ጎቶ ሲገደል በሚያሳየው የአይሲስ ቪዲዮ ውስጥም፣ ይሄው ግለሰብ ግድያውን ሲፈጽም እንደታየ ዘገባው አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ የግድያ ተግባሩን ሲፈጽም ሙሉ ለሙሉ ጥቁር ልብስ ለብሶ፣ ፊቱን በጭንብል ጋርዶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ አንገት ከመቅላቱ በፊትም በእንግሊዛውያን የአነጋገር ቅላጼ ምዕራባውያን መንግስታትን ያወግዝ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
በአይሲስ ቁጥጥር ስር ቆይተው በቅርቡ የተለቀቁ የአይን እማኞች፣ ግለሰቡ በሶሪያ ከሚንቀሳቀሱ የቡድኑ እንግሊዛውያን ጂሃዲስት መሪዎች አንዱ እንደሆነ መመስከራቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ