• ያገለገሉ ጐማዎችን ለማስወገድ ወደ አገር ውስጥ ማስገባትም ተከልክሏል
  • የአካባቢ ብክለት የሚያስከትሉ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል

   ለተለያዩ ዕቃዎች መያዣነት ሲያገለግሉ የቆዩትንና አካባቢን በመበከል የጤና እክል ያስከትላሉ የተባሉትን ከ0.03 ሚ.ሜትር በታች የሆኑ ስስ ፌስታሎች ማምረትም ሆነ ከውጭ ማስገባት ተከለከለ፡፡
ፌስታሎቹን ሲያመርቱም ሆነ ሲያስመጡ ባገኘኋቸው ህገወጦች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል የአካባቢና የደን ሚኒስቴር፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ለጋዜጠኞች ባዘጋጀው “የአካባቢ ጥበቃና ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ” ግንዛቤ ማስጨበጫ አውደ ጥናት ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የአካባቢ ህግ ማስከበር ባለሙያ አቶ ግርማ ገመቹ እንደተናገሩት፤ አካባቢን ከብክለት ለመከላከል የሚያስችል የአካባቢ ፖሊሲ በ1989 ዓ.ም ወጥቶ ተግባራዊ መደረግ ቢጀምርም የህጐችን ተፈፃሚነት ለማረጋገጥና በሚደርሱ ጉዳቶች ላይ ተጠያቂነትን ለመፍጠር የሚያስችል አሠራር ባለመኖሩ እንዲሁም የከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ህግ ባለመከበሩ የከተማው ቆሻሻ ለሰዎች እጅግ አደገኛ ሊሆን ችሏል፡ ለዚህም ዋንኛውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት በአገሪቱ በስፋት በጥቅም ላይ የሚውሉትና እንደ ቀልድ በየስፍራው የሚጣሉት ስስ ፌስታሎች ናቸው፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር በ2005 ዓ.ም ጥናት ማድረጉን የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ በጥናቱም በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ እየተመረቱ ወይንም ከውጪ አገር እየገቡ ጥቅም ላይ የሚውሉት ስስ ፌስታሎች በአካባቢው ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዘላቂነት ያለውና እጅግ አደገኛም እንደሆነ መረጋገጡን ገልፀዋል፡፡ ስለዚህም እነዚህ ፌስታሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል ያሉት ባለሙያው አሁን ፌስታሎቹን በሚያመርቱና ከውጪ አገር እያስገቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በሚያደርጉ ሰዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ውፍረቱ 0.03 ሚ.ሜ እና ከዚህ በታች የሆኑ ፕለስቲኮችን ማምረት፣ ማሰራጨትና ከውጪ አገር ማስገባት በጥብቅ መከልከሉንና በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ህገወጦችን ህብረተሰቡ ጥቆማ በማድረግ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ህጋዊ ፌስታል አምራቾች በምርቶቻቸው ላይ ስለምርቱ አወጋገድ ምልክት እንዲያስቀምጡና የአምራቹን አድራሻ በግልጽ እንዲጽፉ ግዴታ መጣሉንም ገልፀዋል፡፡
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ አንቀጽ ዘጠኝ ያገለገለ ጐማን ለማስወገድ ወደአገር ውስጥ ማስገባት የተከለከለ መሆኑን እንደሚጠቁም የገለፁት አቶ ግርማ፣ ቀደም ሲል ከተለያዩ አገራት ገንዘብ እየተከፈለ እንዲወገዱ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ያገለገሉ ጐማዎችን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የሚሰሩ ሰዎች ከፍተኛ ክምችት እንዲፈጠር በማድረጋቸው ምክንያት ያገለገሉ ጐማዎችን ለማስወገድ ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱ እንዲቀር መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ነባር ምግብ ቤቶች የቆሻሻ አያያዛቸውን ኦዲት ማድረግና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድና አያያዝ እቅድ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ህጉ እንደሚያስገድዳቸውም አቶ ግርማ ገልፀዋል፡፡
የኢንዱስትሪዎች ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ነባር ኢንዱስትሪዎች ብክለታቸውን ለማስወገድ የሚያስችል አቅም እስከሚፈጥሩ ድረስ የእፎይታ ጊዜ ሰጥቷቸው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ግርማ፣ የእፎይታ ጊዜው በመጠናቀቁ ምክንያትም ሰሞኑን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ መውሰድ መጀመሩንና እርምጃው ፋብሪካዎቹን እስከመዝጋት የሚደርስ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ 

Published in ዜና

ባለፉት 20 ዓመታት በመላው ዓለም በጐዳና ላይ ሩጫ፣ በማራቶን፤ በግማሽ ማራቶን እና ሌሎች ውድድሮች ላይ ከተሰጡ የገንዘብ ሽልማቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች እስከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰባቸውን ለማወቅ ተቻለ፡፡ በኤአርአርኤስ ድረገፅ ከ1980-2015 እ.ኤ.አ በተሰጡ የሽልማት ገቢዎች  በቀረበው  መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች በተለይ ውጤታማ በሆኑባቸው ያለፉት 20 ዓመታት በወንዶች 29‚048‚658 ዶላር በሴቶች 29‚090‚527 ዶላር እንደሰበሰቡ ተመዝግቧል፡፡
በሌላ በኩል የ2015 እ.ኤ.አ የውድድር ዘመን ከገባ ወዲህ  በመላው ዓለም በተካሄዱ የጐዳና ላይ ሩጫ፤ የማራቶንና የግማሽ ማራቶን ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በሰበሰቡት የሽልማት ገንዘብ ዓለምን እየመሩ ናቸው፡፡ 2015 እ.ኤ.አ ከገባ በኋላ በመላው ዓለም በተደረጉ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች በወንዶች ምድብ 909‚490 ዶላር በመሰብሰብ ሲመሩ፤ የኬንያ በ496‚625 ዶላር ፣  የአሜሪካ በ235‚035 ዶላር፣ የኡጋንዳ በ40‚630 ዶላር፣ የሞሮኮ በ21‚460 ዶላር፣ የጣሊያን በ21‚350 ዶላር እንዲሁም የኤርትራ አትሌቶች በ14‚955 ዶላር ከ2-7 ያለውን ደረጃ አከታትለው ይወስዳሉ፡፡ በሴቶች ምድብ  የኢትዮጵያ አትሌቶች መሪነቱን የያዙት በ857‚975 ዶላር ነው፡፡ የኬንያ በ369‚430 ዶላር፣ የአሜሪካ በ217‚530 ዶላር፣ የኮሪያ ሪፖብሊክ በ66‚200 ዶላር፣ የህንድ በ32‚600 ዶላር፣ የእንግሊዝ በ20‚165 ዶላር እንዲሁም የጣልያን በ18370 ዶላር ከ2-7 ያለውን ደረጃ በሽልማት ገቢያቸው አግኝተዋል፡፡
ባለፉት 35 ዓመታት በወንዶች ምድብ የኬንያ አትሌቶች 86‚407‚048 ዶላር ገቢ በማግኘት በአንደኛ ደረጃ ሲቀመጡ፣ የአሜሪካ አትሌቶች በ30‚653‚055 ዶላር፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች በ29‚048 658 ዶላር ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይወስዳሉ፡፡ የሞሮኮ በ5‚ 608 ‚104፣ የሜክሲኮ በ5‚277‚ 483፣ የደቡብ አፍሪካ በ4 ‚691 ‚978፣ የጣሊያን በ3‚ 417‚ 841፣ የብራዚል በ3‚003‚132፣ የእንግሊዝ በ2‚769‚842 ዶላር ገቢያቸው እስከ 10ኛ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡  በሴቶች ምድብ ደግሞ ባለፉት 35 ዓመታት በሰበሰቡት የሽልማት ገቢ አንደኛ ደረጃ  በአትሌቶቿ 35‚332‚043 ዶላር ገቢ ያስመዘገበችው አሜሪካ ናት፡፡ ኬንያ በ33‚230‚146 ዶላር ሁለተኛ ደረጃ ስትወስድ ኢትዮጵያ በ29‚090‚527 ዶላር ገቢ ሦስተኛ ሆናለች፡፡ የራሽያ አትሌቶች በ14‚846‚746፣ የእንግሊዝ በ4‚387‚203፣ የጃፓን በ3‚713‚838፣ የሮማኒያ በ3‚691‚270፣ የጀርመን በ3‚592‚710፣ የካናዳ በ3‚552‚047 እንዲሁም የሜክሲኮ በ3‚067‚463 ዶላር ገቢያቸው እስከ 10ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡
የዓለም የጐዳና ላይ ሩጫዎች  የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር (ARRS) በድረገፁ በሚያሰራጫቸው አሃዛዊ መረጃዎች  ከ3000 ሜትር እና ከዚያ በላይ በሆኑ የረጅም ርቀት ሩጫዎች ላይ ያተኩራል፡፡ በኤአርአርኤስ ድረገፅ ላይ ባለፉት 35 ዓመታት በመላው ዓለም የተካሄዱ ከ100ሺ በላይ ውድድሮች ዙሪያ የተመዘገቡ ከ900ሺ በላይ አሃዛዊ መረጃዎችን ተከማችተዋል፡፡ በ35ሺ አትሌቶች የሩጫ ዘመን የተሟላ የመረጃ ስብስብ የሚገኝበት ነው፡፡ ኤአርአርኤስ የሽልማት ገቢ መረጃዎችን በማሰባሰብ ደረጃ ለማውጣት የቻለው በይፋ የሚገለፁ የገንዘብ ሽልማቶችን በመንተራስ በሰራው ስሌት ነነው፡፡ አትሌቶች በውድድር ላይ  በግላቸው፤ በወኪላቸው በመደራደር የሚያገኟቸውን የተሳትፎ ፣ የስፖንሰርሺፕ እና የቦነስ ክፍያዎችን የሽልማት ገቢው አሃዛዊ መረጃ አያካትትም፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ባለፉት 25 ዓመታት በሰበሰቡት የሽልማት ገቢያቸው በኢትዮጵያ ከ1 እስከ 10 የሚኖራቸውና እና ከመላው ዓለም የሚያገኙት ደረጃ እንዲሁም ባለፉት 12 ዓመታት የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ያገኙት የነበረው ድምር የሽልማት ገቢ ከዚህ በታች በሁለት ሰንጠረዦች ቀርቧል፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የደርሶ መልስ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸው ዛሬ የካሜሮን አቻቸውን ያስተናግዳሉ፡፡  ጨዋታው  ባለፈው ሰሞን 12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮናን በብቃት ባስተናገደው አዲስ አበባ ስታድዬም ሲከናወን የስፖርት አፍቃሪው የሚኖረው ድጋፍ ለውጤቱ ማማር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡   የግብፅ ዳኞች ግጥሚያውን እንደሚመሩት ሲታወቅ የጨዋታው ኮሚሽነር ከኬንያ እንደተመደበ ተገልጿል፡፡
ሉሲዎቹ በአሠልጣኝ ኃይሏ ዘለቀ የሚመሩ ሲሆን  26 ተጨዋቾችን በኢትዮጵያ ሆቴል ተሰባስበው ከሁለት ሳምንት በላይ ጠንካራ ዝግጅት አድርገዋል፡፡  ከሁለት ዓመት በፊት ከዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛ መነቃቃት ሊፈጥሩ የቻሉት ሉሲዎቹ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ተነፍጓቸው ቆይተዋል፡፡ ለመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎ በመብቃት ተገቢውን ትኩረት ለመመለስ የሚፋለሙ ይሆናል፡፡
የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ከ3 ወራት በኋላ የሚካሄደው በኮንጎ ብራዛቪል ሲሆን በእግር ኳስ ስምንት ብሄራዊ ቡድኖች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ በማጣርያው 17 አገሮች የተሳተፉ ሲሆን አዘጋጇ ኮንጎ በቀጥታ ስታልፍ ቀሪዎቹን ሰባት ቡድኖች ለመለየት የሁለተኛ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ወሳኝ ይሆናሉ፡፡ ከኢትዮጵያ እና ካሜሮን ባሻገር፤ ማሊ ከናይጄርያ፤ ቦትስዋና ከደቡብ አፍሪካ፤ ጋና ከዚምባቡዌ፤ ታንዛኒያ ከዛምቢያ፤ ጊኒ ቢሳዎ ከአይቬሪኮስት እንዲሁም ግብፅ ከሴኔጋል ሌሎቹ ጨዋታዎች ናቸው፡፡
በወርሃዊው የፊፋ ደረጃ 44ኛ የሆኑት ሉሲዎቹ በአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ 3 ጊዜ ተካፍለዋል፡፡ 11 ጨዋታ አድርገው 1 ድል፤ 4 አቻ እንዲሁም 6 ሽንፈት ገጥሟቸዋል፡፡ በ2002 እኤአ በምድብ ማጣርያ፤ በ2004 እኤአ በአራተኛ ደረጃ እንዲሁም በ2012 እኤአ በምድብ ማጣርያ የተወሰነ ውጤት አላቸው፡፡ የካሜሮን አናብስት በበኩላቸው የፊፋ ደረጃቸው  52ኛ ሲሆን በ2012 እኤአ ለመጀመርያ ጊዜ በኦሎምፒክ እግር ኳስ መሳተፍ የቻሉና በ2015 እኤአ ደግሞ ለመጀመርያ ጊዜ በሴቶች የእግር ኳስ ዓለም ዋንጫ ገብተዋል፡፡ 1991 እኤአ ጀምሮ ለ12 ጊዜያት በአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ተሳትፈውም በ1991 በ2004 እና በ2014 እኤአ ሁለተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡

Saturday, 21 March 2015 10:53

ባሬቶ ይቀጥላሉ!

 6 ወጣቶች ለካምፕ ስልጠና ወደ አውሮፓና አሜሪካ  ይላካሉ
ዋልያዎቹ በ56 ሚ. ብር ዋና ስፖንሰር አግኝተዋል
  በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት መስራት ከጀመሩ 1 ዓመት ሊሞላቸው ወር የቀራቸው ፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከሃላፊነቱ እንዲነሱ  ግፊት ቢደረግባቸውም በሃላፊነታቸው ይቀጥላሉ፡፡ አሰልጣኙ ሊባረሩ  እንደሚችሉ አሉባልታዎች እየተነገሩ ቢቆይም ስለጉዳዩ ምንም የተለየ ነገር እንዳልሰሙ፤ በሚቀጥለው ሰሞን ሚዲያውን በጉዳዩ ላይ ከፌደሬሽኑ ጋር ለማወያየት እንደታሰበና እንደ እቅዳቸው መስራት ባይችሉም በኢትዮጵያ እግር  ኳስ ውስጥ ለማሳካት የፈለጉትን ለውጥ መሰረት ለማስያዝ በጀመሯቸው ተግባራት  ትኩረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ባረፉበት ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ከስፖርት አድማስ ጋር አጭር  ውይይት ያደረጉት አሰልጣኝ ባሬቶ በሃላፊነታቸው ዙርያ ስለተነሳው አሉባልታ ብዙ እንደማይጨነቁ ተናግረው፤ በዓላማቸው ለመስራት የሚያደርጉትን ጥረት እንደቀጠሉ ገልፀዋል፡፡ ይህን ለማስገንዘብም ሲሉ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙበትንና በጥብቅ ክትትል የመለመሉዋቸውን ስድስት ወጣት ተጨዋቾች ለ1 ወር የካምፕ ስልጠና ወደ አሜሪካና ወደ አውሮፓ ለመላክ ማረጋገጫ ማግኘታቸውን አሳውቀዋል፡፡ ከስድስቱ የወደፊት የብሄራዊ ቡድን ተስፋ የሚሆኑ ተጨዋቾች ሁለቱን በአሜሪካ ሜጀር ሶከር ሊግ በሚገኝ ክለብ እንዲሁም  አራቱን በፖርቱጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን አካዳሚ በነፃ 1 ወር የካምፕ  ስልጠና ልምድ እንዲወስዱ  የግል ጥረት አድርገው ተሳክቶላቸዋል፡፡ ተጨዋቾቹን ለብሄራዊ ቡድን ለማዘጋጀት የፈጠርኩት   እድል ነው ያሉት አሰልጣኙ በአሜሪካ ሜጀር ሶከር ሊግ በሚገኝ ክለብ ለሁለት ወጣት ተጨዋቾች ሁኔታውን ያመቻቹት ለስብሰባና ለስልጠና በሄዱበት ወቅት ባደረጉት ምክክር እንደሆነ ገልፀው፤ የፖርቱጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን አካዳሚ ደግሞ ለ10 ዓመታት በሰጡት ግልጋሎት ላቀረቡት ማመልከቻ ተገቢውን ድጋፍ እንደሰጣቸው ለስፖርት አድማስ ተናግረዋል፡፡ ከስድስቱ ተጨዋቾች ሁለቱ በበረኛነት የሚጫወቱ እንደሆነ የጠቆሙት ባሬቶ ሁሉም በካምፕ ቆይታቸው ለ30 ቀናት በፕሮፌሽናል ክለብ በሚሰሩት የስልጠና መርሃ ግብር የማነቃቂያ ልምድ ያገኛሉ ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ከሄኒከን ኩባንያ ጋር በመመካከር በእረፍት ቀናት በአበበ ቢቂላ ስታድዬም በርካታ ታዳጊ ቡድኖች የሚሳተፉባቸው ውድድሮችን በየሳምንቱ በማዘጋጀትና በቅርብ ክትትል በመስራት ለዘላቂ ለውጥ መነሻ የሚሆን የእድገት ስትራቴጂ ለመጀመር እየሰሩ መሆናቸውንም አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ለስፖርት አድማስ ተናግረዋል፡፡ “በየእሁዱ 300 ልጆች ወደ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም እንዲመጡ እጠብቃለሁ፡፡ ሜዳውን ለ3 እከፍልና 7ለ7 ሆነው እየተቧደኑ በአንድ አሠልጣኝ እየተመሩ ሲጫወቱ ለማየት ጉጉት አለኝ፡፡ ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎች በቶሎ ተመልክቶ ለመሥራት የሚያግዝ የውድድር ዓይነት ነው፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ብዙ የሉም እንጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ መሠራት ያለበት ነው፡፡ ወደፊት በስፋት እንዲሠራበት ማነቃቃት እፈልጋለሁ፡፡ ልጆችን ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም እድል መስጠት ለእያንዳንዱ ቡድን ኳስ ለመስጠትና ማሊያና ምግብ ለማቅረብ የበኩሌን ጥረት እያደረኩ ነው፡፡ ከሁሉም ሰው ጋር ግልጽ ግንኙነት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ ወደዚህ ስመጣ በወጣቶች እግር ኳስ ልማት ላይ የመሥራት ዋና አላማ ነበረኝ፡፡” ሲሉም ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ሀ-17 ሊግ መጀመሩን አውቃለሁ የሚሉት ማሪያኖ ባሬቶ፤ ቅድምያ ተሰጥቶ መሠራት ያለበት በሀ-21 መሆን እንደነበረበት ገልፀው፤ ወደ ብሔራዊ ቡድን ወጣቶችን ለማሳደግ የሚያመች አሠራር መኖሩ እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ተናግሬያለሁ ብለዋል፡፡  ሥራዬን በ23 ምክንያቶች መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ እንደምክንያትም የወጣት ተጨዋቾችን ሥም ዘርዝረዋል፡፡ ታሪኩ ፣ ኪብሮም፣ አንዳርጋቸው፣ ናትናኤል፣ ዳዊት፣ ራምኬል፣ አብዱልከሪም…ወዘተ በማለት ለእነሱ ተጨዋቾች የማልታገለው ፈተና የለም በማለት፡፡ ኢትዮጵያውያን በሥራዬ ደስተኛ እንደሆኑ ነው የምረዳው፡፡ ተጨዋቾቼም ደስተኛ ናቸው፡፡ የውጭውን እድል የሚያገኙ ወጣቶችን ምርጫ የማደርገው እራሴው ነኝ፡፡ የማማክረው ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችን የማከናወን ፍላጐት አለኝ የሚሉት አሠልጣኙ፤ በተለይ በቅርቡ የቼልሲ ክለብ አካዳሚ ለመጐብኘት ቀጠሮ ይዣለሁ ብለው ለስፖርት አድማስ ሲናገሩ ከሞውሪንሆ ጋር በጣም ጓደኛሞች መሆናቸው እና በጉብኝታቸው ወቅት በክለቡ አካዳሚ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ያሉትን እድሎች መመልከት እንዳሰቡ ገልፀዋል፡፡
በተያያዘ ሔኒከን ቢራ ፋብሪካ ዋልያዎቹን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በዋልያ ቢራ እና ድራፍት ምርቶቹ በዋና ስፖንሰርነት በ56 ሚሊዮን ብር ለመደገፍ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከትናንት በስቲያ ተፈራርሟል፡፡ በስምምነቱ ዋልያ ቢራ እና ድራፍት የብሄራዊ ቡድኑ ዋና ስፖንሰር ሆኖ  በየዓመቱ 14 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያበረክት ሲገለፅ የብሄራዊ ቡድኑን ውጤታማነት   እንደሚደግፍም ታውቋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ያገኘው የስፖንሰርሺፕ ገቢ በአሰልጣኙ መነሳት ላይ የተፈጠረውን ግፊት አብርዶታል፡፡
ፌዴሬሽኑ ከሳምንት በፊት ለመገናኛ ብዙሃናት ባደረሰው አጭር መግለጫ በማርያኖ ባሬቶ ዙርያ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳኔም ሆነ በጉዳዩ ዙሪያ የተነጋጋረበት ሁኔታ አለመኖሩን  ገልፆ ነበር፡፡ በዋና አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ጉዳይ ላይ በአፈጻጸም ሪፖርቶችና ሙያዊ ግምገማዎች ላይ በመመስረት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚከተለውን አቅጣጫ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን በወቅቱ እንደሚያደርስም በወቅቱ መግለፁ አይዘነጋም፡፡ ይህን ተከትሎ ፖርቱጋላዊው አሠልጣኝን በተመለከተ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ትናንት ተሰብስቦ የነበረ ሲሆን በአሰልጣኙ መነሳትና መቀጠል ዙርያ ምን ውሳኔ እንዳሳለፈ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፖርቱጋላዊው የ58 አመት አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ  በ2 አመት ኮንትራት ለማሰራት መፈራረሙ የሚታወስ ነው፡፡  
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኃላፊነት ያስቀመጣቸው የቴክኒክ ዲፓርትመንትና ቴክኒክ ኮሚቴ ከአሠልጣኙ ጋር ግንኙነታቸው የሻከረ መሆኑ  ጫና እንደፈጠረ የሚገለፅ ሲሆን፤ በዋናው ብሄራዊ ቡድን ወደ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ  ባለመቻሉና ከዚያም በኋላ ከ23 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንን በመምራት  ከመላ አፍሪካ ጨዋታዎች  በመቅረታቸው በአንዳንድ ሚዲያዎች እና የስፖርት አፍቃሪዎች ከሃላፊነታቸው ይነሱ የሚለው አጀንዳ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖባቸዋል፡፡  አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ከሶስት ሳምንት በፊት ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ፌደሬሽኑ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በነበሩ እቅዶች መስራት እንዳለባቸው ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡  አሰልጣኙ ዋናው ብሄራዊ ቡድኑ በሃላፊነት ለመምራት ሲረከቡ   እቅዳቸው በወጣቶች ላይ መስራት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡   ከ7 በላይ የሚሆኑ ወጣት ተጨዋቾችን ወደ ዋናው ብሄራዊ ቡድን  በማሳደግ  ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ማርያኖ ባሬቶ በቆይታቸው በነጥብ ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉት አንድ ጨዋታ ብቻ መሆኑ ብሄራዊ ቡድኑ እና ወጣት ብሄራዊ ቡድኑ በሜዳው ማሸነፍ አለመቻሉም ተተችቷል፡፡ በአጠቃላይ 19 ጨዋታዎች ተጫዉተው በ12ተሸንፈው በ4ቱ አቻ ወጥተው 3ቱን አሸንፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ታሪክ ባለፉት 56 ዓመታት ከ20 በላይ አሰልጣኞች በሃላፊነቱ የተፈራረቁ ሲሆን ከእነሱ መካከል ባሬቶን ጨምሮ ከስምንት አገራት የተውጣጡ 10 የውጭ አገር አሰልጣኞች ሰርተዋል፡፡ የውጭ አገር አሰልጣኝ በአፍሪካ ደረጃ ለሚይዘው ብሄራዊ ቡድኑ በአማካይ እስከ  4 ዓመታት የሚቆይ የስራ ኮንትራት ማስፈለጉ ቢገለፅም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሩት አንዳቸውም በሃላፊነቱ ከሁለት ዓመታት በላይ አልቆዩም፡፡ ከማርያኖ ባሬቶ በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ማሰልጠን የቻሉ የውጭ አገር አሰልጣኞች መካከል   በ1959 ለሁለት አመታት የቼኮስላቫኪያው ጂሪ ስታሮስታ ፤ በ1961 እኤአ አንድ አመት ላልሞላ ጊዜ የዩጎስላቪያው ስላቫኮ ሚሎሶቪች፤በ1968 ሃንጋሪያዊው ስዙክስ ፈርኔክ ለ1 ዓመት፤ በ1974 ጀርመናዊው ፒተር ሽትናይገር ለሁለት ዓመት ፤ በ1988  ጀርመናዊ ክላውስ ኢግናሃብሰን ለአንድ አመት ፤ በ2002 ጀርመናዊው ጆሃን ፊገ ለ10 ወራት፤ በ2006 እኤአ ፈረንሳዊው ዲያጎ ጋርዚያቶ ለ14 ወራት፤ በ2010 እኤአ ስኮትላንዳዊው ኢፊ ኦኑራ ለ9 ወራት፤ በ2011 ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌንት ለ6 ወራት ብቻ እንደሰሩ ከብሄራዊ ቡድኑ የታሪክ መዝገብ ለመረዳት ይቻላል፡፡

Saturday, 21 March 2015 10:49

ያልተጠበቀው ሲሳይ

    ባለፈው ረቡዕ ረፋዱ ላይ የእስራኤል የምርጫ ቦርድ የምርጫውን ውጤት ይፋ አደረገ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሚመራው የሊኩድ ፓርቲ 30 መቀመጫዎች አግኝቶ ማሸነፉና በይስሀቅ ሔርዞግ የሚመራው የጽዮናውያን ህብረት ፓርቲ ደግሞ 24 መቀመጫዎች በማግኘት ሁለተኛ መውጣቱ ተረጋገጠ፡፡
የፓርቲያቸውን የምርጫ ውጤት ለማወቅ ገና በጠዋቱ በፓርቲያቸው ጽ/ቤት ደጅ ላይ የተሰባሰቡት የሊኩድ ፓርቲ ደጋፊዎች የሰሙትን ማመን አልቻሉም፡፡ በእየሩሳሌም ምስራቅ የወረዳ ሶስት የሊኩድ ፓርቲ የቅስቀሳ አስተባባሪ የነበረው የ24 ዓመቱ ዳን ሞርዶካይ በሰሙት የምርጫ ውጤት ተገርመው አፋቸውን ይዘው የቆሙትን ጓደኞቹን በከፍተኛ የደስታ ስሜት እያቀፈ፤ “ይህ የማይታመን ነገር ነው! ይህ ከአምላክ የወረደልን ያልተጠበቀ ሲሳይ ነው!” በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የሊኩድ ፓርቲ ደጋፊዎች የፓርቲያቸውን የምርጫ ውጤት ማመን ቢያቅታቸውም ሆነ ዳን ሞርዶካይ ውጤቱ ያልጠበቁት ሲሳይ መሆኑን በመግለፅ በደስታ አቅሉን ስቶ ጮቤ ቢረግጥ ፈጽሞ አይፈረድባቸውም፡፡
ምርጫው ተጀምሮ እስከተጠናቀቀበት ያለፈው ማክሰኞ ድረስ በተለያዩ ጋዜጦች ታትመው የወጡ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች በቤንያሚን ኔታንያሁ የሚመራው ወግ አጥባቂው የሊኩድ ፓርቲ በምርጫው አብላጫ ድምጽ ማግኘት እንደማይችልና ይስሀቅ ሄርዞግ በሚመሩት የፂዮናውያን ህብረት ፓርቲ እንደሚረታ የተነበዩ ብዙዎች ነበሩ፡፡ በዚህ የተነሳም የአብዛኞቹ የሊኩድ ፓርቲ ደጋፊዎች የእናሸንፋለን ስሜታቸው በእጅጉ የተቀዛቀዘ ነበረ፡፡
የምርጫው ውጤት ግን የቅድሚያ ግምቶችን ሁሉ ከመሰረታቸው ፉርሽ በማድረግ፣ ያ ሁሉ የእስራኤል ጋዜጣ በየእለቱ ያራገበው የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ስህተት መሆኑን በድጋሚ ማረጋገጥ ቻለ፡፡
በዚህ የእስራኤል ምርጫ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና እውቅ ፖለቲከኞች ተካፍለውበታል፡፡ ከቤንያሚን ኔታንያሁ፣ ይስሀቅ ሄርዞግ፣ ዚፒ ሊቭኒና ከሞሸ ካህሎን ልቆ በምርጫው መድረክ ላይ በዋናነት የተወነ የፖለቲካ መሪ ግን አንድም አልነበረም፡፡
ከምርጫው በፊትም ሆነ በምርጫው ወቅት አብዛኛው የእስራኤል ህዝብ ከፍልስጤማውያን ጋር በሰላምና በትብብር መኖር እንደሚፈልቅ በግልጽ ይነገርለት ነበር፡፡ እናም ይህንን አቋም ለሚያራምደውና በይስሀቅ ሄርዞግና በዋነኛ ተባባሪያቸው ዚፒ ሊቭኒ ለሚመራው የፂዎናውያን ህብረት ፓርቲ የድጋፍ ድምፃቸውን በመስጠት ለአሸናፊነት ያበቁታል ተብሎ በእርግጠኛነት ተገምቶ ነበር፡፡
የማታ ማታ በአሸናፊነት የወጡት ግን ከፂዎናውያን ህብረት ፓርቲ በተቃራኒው በፍልስጤማውያንና በኢራን ላይ ብዙዎች “ጽንፈኛ” በሚል የፈረጁትን አክራሪ አቋም የሚያራምዱት የሊኩዱ መሪ ቤንያሚን ኔታንያሁ ናቸው፡፡
አንድ መቶ ሀያ መቀመጫ ካለው የእስራኤል ክኔሴት (ፓርላማ) ሰላሳውን ያገኘው የሊኩድ ፓርቲ፤ የሱ ቢጤ ከሆኑ የቀኝ ክንፉ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች ጋር በመሆን የጥምር መንግስት የመመስረት እድሉን በእጅጉ ማስገባት ችሏል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቤንያሚን ኔታንያሁ ለአራተኛ ጊዜ እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመሩ ያስችላቸዋል፡፡ በዚህም የእስራኤል የፖለቲካ የታሪክ መዝገብ፣ ቤንያሚን ኔታንያሁን እስራኤልን ለረጅም ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩ ብቸኛው ሰው ብሎ በክብር ይመዘግባቸዋል፡፡
ከ15 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ነው በተባለለትና ለምርጫው ከተመዘገበው ህዝብ 71.8 በመቶ ያህሉ ድምጽ በሠጠበት በዚህ የእስራኤል ምርጫ ያልተጠበቁ ሌሎች ውጤቶችም ተከስተዋል፡፡ በምርጫው ከተወዳደሩት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት የቻሉት አስር ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ከ23 ዓመት ወዲህ ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ፓርላማ የገቡበት ምርጫ እንዲሆን አድርጎታል፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በእስራኤል የምርጫ ታሪክ 28 ሴቶችና 17 አረብ እስራኤላውያን በየፓርቲያቸው አማካኝነት የፓርላማ መቀመጫ ማሸነፍ የቻሉት በዚህኛው ምርጫ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በዚህ ምርጫ ያልታሰበ ሲሳይ እንደወረደላቸው በግልጽ የተረዱት እንደ ዳን ሞርዶካይ አይነቶቹ የሊኩድ ፓርቲ ደጋፊዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ቤንያሚን ናታንያሁም የድሉን ብስራት ለመጋራት ለተሰበሰቡ በሺ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ረቡዕ እለት ባደረጉት ንግግር እማኝነታቸውን በግልጽ አነጋገር ፊት ለፊት ገልፀዋል፡፡
ይህ ሁሉ ነገር ከእንግዲህ ታሪክ ነው፡፡ አሁን የእስራኤላውያንንም ሆነ የእስራኤልን ጉዳይ ነገሬ ብለው በጥሞና ለሚከታተሉተ ሁሉ ዋናውና የላቀው ጉዳይ ከዚህ በሁዋላ የሚመጣው ነገር ነው፡፡
የቤንያሚን ኔታንያሁ ለአራተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መመረጥ እስራኤልን ከተቀረው ዓለም ጋር ፍጥጫ እንድትገጥም በሚያደርጋት አውራ ጎዳና መሀል ላይ አስቀምጧታል፡፡ ቤንያሚን ኔታንያሁ የጥምር መንግስት የሚያቋቁሙት እንደ ሊኩድ ፓርቲ ሁሉ የፍልስጤምን ነፃ መንግስት መቋቋም ከሚቃወሙ የቀኝ ክንፉ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች ጋር ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለራሷ ለእስራኤልም ሆነ ለመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ሰላም መጠበቅ ምንም አይነት ፋይዳ የሌለው ይልቁንም የባሰ አደጋና አለመረጋጋት የሚጋብዝ ግብአት ነው፡፡
እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዲፈጠር ደግሞ የአብዛኛው የዓለም ህብረተሰብ በተለይ ደግሞ እንደ አሜሪካ ያሉ ሀያል ሀገራት ፍላጎትም ሆነ ምኞት አይደለም፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የአይሲስ እስላማዊ ጀሀድ ቡድን በፈጠረባቸው መጠነ ሰፊና አስጨናቂ ስጋት እየተናጡ ባለበትና የምዕራቡ አለምም ይህንን እኩያ የለሽ ጽንፈኛ እስላማዊ መንግስት ለመቋቋም ወዲያ ወዲህ በሚልበት በአሁኑ ወቅት፣ እስራኤል ይህን የመሰለ ግትር አቋም ይዛ ለመቀጠል መፈለጓ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ መገለልን እንዳያተርፍላት ብዙዎች ገና ከአሁኑ ሰግተዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ግጥሚያው የምር አይደለም ተብሏል
  የቀድሞው የማሳቹሴትስ ገዢና የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ ሚት ሩምኒ  ከቀድሞው የከባድ ሚዛን ቦክስ የአራት ጊዜ የአለም ሻምፒዮን ኢቫንደር ሆሊፊልድ ጋር ቦክስ ሊጋጠሙ ነው ሲል ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
በመጪው ግንቦት 15 ሶልት ሌክ ሲቲ በተባለችው የአሜሪካ ከተማ የሚከፈት አንድ ኤግዚቢሽን አካል እንደሚሆን የተነገረለት ይህ የምር ያልሆነ የቦክስ ግጥሚያ፣ አላማው ለድሃ አገራት ዜጎች የአይን ቀዶ ህክምና አገልግሎት ለሚሰጠው ቻሪቲ ቪዥን የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ገቢ ማሰባሰብ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ የዓለም ሻምፒዮኑን ቡጢኛ ለመግጠም ቆርጠው እንደተነሱ የገለጹት የ68 አመቱ ፖለቲከኛ ሚት ሩምኒ፣ ፍልሚያው በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ አለበት፣ ያለዚያ አፈር ድሜ መግባቴ አይቀሬ ነው ሲሉ ስጋታቸውን አበክረው ገልጸዋል፡፡
ከ18 አመታት በፊት ከታዋቂው ቦክሰኛ ማይክ ታይሰን ጋር ባደረገው ግጥሚያ አንድ ጆሮውን በከፊል ያጣው የ52 አመቱ ኢቫንደር ሆሊፊልድ፣ ከ3 አመታት በፊት ከባራክ ኦባማ ጋር የፖለቲካ ፍልሚያ አካሂደው ከተረቱት ሚት ሩምኒ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ ከወዲሁ በጉጉት እየተጠበቀ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ለ20 አመታት ያገለገለው ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር በፕሮጀክት ስፓርታን ይተካል
ታዋቂው ማይክሮሶፍት ኩባንያ እጅግ የተራቀቀ የተባለለትን አዲሱ ዊንዶውስ 10 ኦፐሬቲንግ ሲስተም በመጪዎቹ አራት ወራት ጊዜ ውስጥ በይፋ በማስተዋወቅ በስራ ላይ እንደሚያውል ገለጸ፡፡
በአለም ዙሪያ ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የሚነገርለትንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ  አዳዲስ አሰራሮችን በመላበስ በመቅረብ ላይ የሚገኘውን ዊንዶውስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም የሚያመርተው ማይክሮሶፍት ምክትል ፕሬዚዳንት ቴሪ ሜርሰንን ጠቅሶ ቴሌግራፍ እንደዘገበው፣ ኩባንያው አዲሱን ኦፐሬቲንግ ሲስተም እስከ ግንቦት ወር መጀመሪያ በስራ ላይ ለማዋል አቅዷል፡፡
አዲሱ ኦፐሬቲንግ ሲስተም በ111 የተለያዩ ቋንቋዎች እንደሚዘጋጅና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ 190 አገራት የኩባንያው ደንበኞች እንደሚዳረስ የጠቆመው ዘገባው፣ ኦፐሬቲንግ ሲስተሙ ነባሮቹን ዊንዶውስ 7፣ 8.1 እና ዊንዶውስ ፎን 8.1 ለሚጠቀሙ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞች ለአንድ አመት ያህል በነጻ እንደሚሰጥም አስታውቋል፡፡
ዊንዶውስ 10 በዴስክቶፕ እና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ላይ እንዲሁም የማይክሮሶፍት ኩባንያ ምርቶች በሆኑ ታብሌቶችና የሞባይል ስልኮች ላይ እንደሚሰራ ያስታወቀው ኩባንያው፣ ለ20 አመታት ያህል አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን ነባሩን ሰርች ኢንጂን ኢንተርኔት ኤክስፕሎረርን፣ ፕሮጀክት ስፓርታን በተሰኘ አዲስ ፈጠራው መተካቱንም ጠቁሟል፡፡
ኢንተርኔት ኤክስፕሎረር ምንም እንኳን በመላው አለም የሚገኙ ከ1 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ታዋቂ ሰርች ኢንጂን ቢሆንም፣ ተሻሽለው ከተሰሩትና ከፈጣኖቹ ፋየርፎክስ እና ጎግል ክሮም ጋር መወዳደር ባለመቻሉ፣ ኩባንያው ፕሮጀክት ስፓርታን የተሰኘውን አዲሱን ሰርች ኢንጂን ለመስራት መወሰኑንም ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Saturday, 21 March 2015 10:43

የየአገሩ አባባል

የተከፈተ አፍ ፆሙን አያድርም፡፡
ረዥሙም ዛፍ እንኳን እግሩ ስር የሚጠብቀው መጥረቢያ አለ፡፡
ሁሉም ድመት በጨለማ ጥቁር ነው፡፡
ሞኝ ሃብትን ሲያልም፤ ብልህ ደስታን ያልማል፡፡
የምግብ ፍላጎቱ የተከፈተለት ሰው፣ ማባያ አይፈልግም፡፡
ጥሩ ባልንጀራ ረዥሙን መንገድ ያሳጥራል፡፡
ልማድ ከብረት የተሰራ ሸሚዝ ነው፡፡
ባዶ ሆድ ጆሮ የለውም፡፡
ንዴት መጥፎ አማካሪ ነው፡፡
በአንዴ ሁለት አጋዘኖችን የሚያሳድድ ጅብ ፆሙን ያድራል፡፡
በእጅህ ዱላ ይዘህ ውሻን አትጥራ፡፡
የመፍትሄው አካል ካልሆንክ የችግሩ አካል ነህ፡፡
ሞኝ ሲረገም የተመረቀ ይመስለዋል፡፡
ከሰፈሩ ወጥቶ የማያውቅ ፣ እናቱ የባለሙያ ቁንጮ ትመስለዋለች፡፡
ታላላቆችን የሚያከብር ለራሱ ታላቅነት መንገዱን ይጠርጋል፡፡
ዓለም ለማንም ተስፋ (ቃል) አትሰጥም፡፡
ሌሊቱ ምን ቢረዝም መንጋቱ አይቀርም፡፡
ሳይወለድ ትችትን የሚፈራ ህፃን ጨርሶ አይወለድም፡፡
ከሴት ጋር ማውራት የማይወድ፣ ወንደላጤ ሆኖ ይቀራል፡፡
አባወራው መሬት ላይ የተቀመጠበት ቤት ውስጥ ወንበር እንዲሰጥህ አትጠብቅ፡፡
ወፍ በመመላለስ ብዛት ጎጆዋን ትሰራለች፡፡
የውሃውን ጥልቀት በሁለት እግሮቹ የሚለካ ሞኝ ብቻ ነው፡፡
የጅብ ዣንጥላ ይዞ የተመለሰ አዳኝን ስለአደኑ አትጠይቀው፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

በወጣት ገጣሚ እምሻው ገ/ዮሃንስ የተጻፈው “የአመድ ልጅ እሳት” የተሰኘ የግጥሞች ስብስብ መጽሃፍ፣ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በገበያ ላይ መዋሉን ገጣሚው በተለይ ለአዲስ አድማስ ገለጸ።
በተለያዩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 60 ያህል ግጥሞችን የያዘውና በ68 ገጾች የተቀነበበው የግጥም ስብስብ መጽሃፉ፣ የመሸጫ ዋጋው 20 ብር ሲሆን፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚገኙ የመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች እንዲሁም በማህበራዊ ድረ-ገጽ መጽሃፍት አቅራቢዎች እየተሸጠ ይገኛል፡፡
በደብረ ማርቆስ ከተማ በተካሄዱ የስነ-ጽሁፍ ውድድሮች በተደጋጋሚ በማሸነፍና ለተለያዩ ድምጻውያን የዘፈን ግጥሞችን በመስጠት  የሚታወቀው ገጣሚው፣ ከዚህ በፊትም “ብላቴና” የተሰኘና ለህጻናት በሚመጥን መልኩ የተዘጋጀ የግጥም መጽሃፍ ለንባብ አብቅቷል። ገጣሚ እምሻው ገ/ዮሃንስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ያቀርባቸው በነበሩ ወጎችና ግጥሞቹም ይታወቃል።

የ6 ሰዓሊያን ሥራዎች ለዕይታ ይቀርባሉ
   የስድስት ሰዓሊያን ስራዎች ለዕይታ የሚቀርቡበት “ታዛ አርት ኤግዚቢሽን” በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ ቫቲካን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው ታዛ ጋለሪ እንደሚከፈት ተገለፀ፡፡
የስዕል ኤግዚቢሽኑ ከመጋቢት 12 እስከ 26 ቀን 2007 ዓ.ም ለአስራ አራት ቀናት፣ ከማክሰኞ እስከ እሁድ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ለእይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል ተብሏል፡፡ በ “ታዛ አርት ኤግዚቢሽን” የሰዓሊ ሱራፌል አማረ፣ ንፁሰው ተረፈ፣ ለይኩን ወንድይፍራው፣ ንጋቱ ሰለሞንና ዮናታን ወንድወሰን የሥነጥበብ ሥራዎች እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ የአሁኑ ኤግዚቢሽን ለታዛ አርት ጋለሪ ሁለተኛው ሲሆን የመጀመሪያው “አዲስ አበባ ቤቴ” በሚል ርዕስ እንደቀረበ ተገልጿል፡፡ በየሁለት ወሩ አዳዲስ የስዕል ኤግዚቢሽኖችን ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጋለሪው በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Page 5 of 21