Monday, 16 March 2015 09:59

የአዲስ አድማስ ምስጋና

ባለፈው ሰኞ በብሔራዊ ቴአትር በተከበረው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የ15ኛ ዓመት በዓል ዝግጅት ላይ ግጥምና ሙዚቃ በማቅረብ፣ እንዲሁም ፕሮግራሙን ስፖንሰር በማድረግ ድጋፋችሁን ለሰጣችሁን ሁሉ ልባዊ ምስጋናችንን ልናቀርብ እንወዳለን፡፡
በዝግጅቱ ላይ በመታደም በዓላችንን ላደመቃችሁልን የአዲስ አድማስ ወዳጆችም ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡
ዝግጅት ክፍሉና ማኔጅመንቱ

በ“ሉጬ” መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ በሳሬም ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “ምህረት” የተሰኘው ፊልም ባለፈው ማክሰኞ በአቤል ሲኒማ ቤት ተመረቀ፡፡ በፈድሉ አወል ተደርሶ ፕሮዱዩስ የተደረገው ፊልሙ፤ዮናስ ሉጬ ዳይሬክት እንዳደረገው ታውቋል። የ1፡32 ርዝማኔ ያለውን ይሄን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ 10 ወራትን ፈጅቷል ብሏል፡፡ የፊልሙ ታሪክ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ለ20 ዓመታት ተደብቆ የኖረ ምስጢር ልጃቸውን አሜሪካ ለመላክ በተደረገ የDNA ምርመራ ሲጋለጥ የሚያስቃኝ ነው፡፡ ልብ አንጠልጣይ የቤተሰብ ድራማ ዘውግ ባለው በዚህ ፊልም ላይ ሽመልስ አበራ፣ ገነት ንጋቱ፣ መንገሻ ተሰማ፣ ባህሬን ከድር፣ ሶፊያ መሃመድና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡ ፊልሙ በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች መታየት እንደጀመረም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በገጣሚ ደመረ ብርሃኑ የተፃፉ የግጥም ስብስቦች የተካተቱበት “በወዜ ወ ባዋዜ” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ ግጥሞቹ በማህበራዊ፣ መንፈሳዊ፣ በፍቅርና ስነልቦና ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ አፍሪካዊ መሆኑ ለግጥሞቹ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ማግኘት እንዳስቻለው በመጽሐፉ ማስታወሻ ላይ የገለጸው ገጣሚው፤አውሮፓዊ ቢሆን ስለቴክኖሎጂ ግጥም መፃፍ ስሜት ስለማይሰጥ “ገጣጣ” ይሆን እንደነበር ጠቁሞ ቻይናዊ ሆኖ ቢፈጠር ደግሞ ከገጣሚነት ይልቅ የባቡር ገጣጣሚ ለመሆን ወደ ኢትዮጵያ ይመጣ እንደነበር ገልጿል፡፡ መፅሃፉ፤ 74 ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን ለአገር ውስጥ በ30 ብር፣ለውጭ በ15 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ገጣሚ ደመረ ብርሃኑ የአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ በተካሄደ የግጥም ውድድር ሁለተኛ ወጥቶ ባለፈው ሰኞ ዘመናዊ የZTE ሞባይል ተሸልሟል፡፡

በደራሲ ቅድስት ይልማ ተፅፎ በኤሊያስ ወርቅነህ ዳይሬክት የተደረገውና በጋላክሲ ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “ገንዘብና ፍቅር 2” ፊልም ዛሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በትሮፒካል ጋርደን ለእይታ እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡ ልብ አንጠልጣይ በሆነው በዚህ የፍቅር ፊልም ላይ ሩታ መንግስተአብ፣ አዚዛ አህመዝ፣ ሜሮን ጌታቸው፣ ኤሊያስ ሁኔን፣ መሳይ ግርማ፣ ደሳለኝ ሃይሉና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡ የ1፡55 ርዝማኔ ያለውን ይሄን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት እንደፈጀ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Monday, 16 March 2015 09:53

ሞልትዋል ብላቴና

(በአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት የግጥም ውድድር 2ኛ የወጣው ግጥም)

ነበር ፍጹም ጨቅላ በጥቁር አፈር ላይ በጥቁር ተፀንሶ
ጥቁር የወለደው ጥቁር ስጋ አልብሶ፣
ነበር ብላቴና
ከጥቁር ገላ ውስጥ ነጭ ወተት ግቶ
አጥንቱ የጸና የቆመ በርትቶ፣ ነበር ደቀ መዝሙር
                  ጥቁር ብላቴና
በነጭ ጠመኔ በጥቁር ሰሌዳ
ሀ ሲሉት ሃ ብሎ A ሲሉት A ብሎ
ጥቁሩን ከነጩ ጋር አዋዶ ያጠና፡፡
ታሪክ የጻፈውን ሳይንስ እያጠፋ
ሳይንስ የፃፈውን ሂሳብ እያጠፋ
ሂሳብ የፃፈውን ሲቪኩ እያጠፋ፤
በተዥጎረጎረች ባንዲት ሰሌዳ ላይ
ሁሉም የእየራሱን ሲያስተምር ሲለፋ
አንዲትዋ ሰሌዳ ጥቁር ወዝዋ ወድሞ
ወጭው የጫረውን ገቢው እያጠፋ
ነበር ብላቴና
ካንድ ወንበር ተቀምጦ ትዝብቱ ያልሰፋ
በሰሌዳው ማድያት በስሎ ያልተከፋ፡፡

Published in የግጥም ጥግ
Monday, 16 March 2015 09:52

የዱበርቲዋ ጀበና

(ለአዲስ አድማስ 15ኛው ዓመት በዓል በተደረገ የሥነ ጽሑፍ ውድድር 2ኛ የወጣ አጭር ልቦለድ)
ዕለተ ሀሙስ፣ ጥቅምት ወር 1998 ዓ.ም፣ ከረፋዱ 5፡15 ይላል፡፡
ከደሴ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ሊይ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ሲያቀኑ ተረግጠዋት የሚያልፉት ትንሽ የገጠር ወረዳ ውስጥ ነው… ይህችው የበሬ ግንባር የምታህል የኩታበር ከተማ በህዝበ አዳም ተጨናንቃለች፡፡ ከከተማዋ እንብርት ላይ ገበያተኛውን የሚያመላልሱ በርካታ አውቶብሦች ተደርድረዋል፡፡ አሁን ግን፣ ሁልጊዜ በዕለተ ሀሙስ ከየቦታው ነቅሎ የሚመጣው ገበያተኛ ወደ የመጣበት እየተመመ ነው፡፡
አንድ የሚያምር “ሥኒከር” ጫማ በጅንስ ሱሪ ያደረገ ወጣት ወደ ደሴ ለመንቀሳቀስ ሞተሩን እያሞቀ ያለውን ተረኛ አውቶብስ ተደግፎ ሲጋራውን ያቦናል። ከወደ ትከሻው ነተብ ብሎ ብዙም የማታሳጣው የቆዳ ጃኬቱም፣ “ሀብታምነቱን” ትለፍፋለች፡፡ በፊት ለፊት ብዙ ገበያተኞች ከሚያውካኩበት አረቄ ቤት ላይ የተተከለት ዐይኖቹ ግን አሁንም አልተነቀሉም፡፡
ሰዓቱን ተመለከተ - አርፍዷል፡፡ የሚጠባበቀው ነጋዴ አሁን በሞቀ ጨዋታ ውስጥ ሆኖ አረቄውን ሲያንጫልጥ እያየ ነው… የዛገ ብረት በመሰለት ጥርሶቹ ሾልኮ፣ ከኩበት ከናፍሩ ጋር እየተላተመ በሚወጣው የሲጋራ ጭስ በአየር ላይ ክብ እየሠራ ተክዟል…
እንዴዬ! ... አይገርምም! ድንገት ግን ነቃ። እንደተነቃቃም ወዲያው፣ ወደሚንቀሳቀሰው አውቶብስ በፍጥነት አመራ፤ በዓይነ ቁራኛ የሚከተለውን ሰው አሁንም አለቀቀውም… በዚች ግርግር በበዛባት ከተማ፣ የሰው ልጅ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት በሚራወጥበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት፣ ወጣቱ “ባለ ጉዳይ” ከዘመኑ መንፈስ የተጋባበትን በአቋራጭ የመክበር ልክፍት ሊያሳካ አቅሉን ስቶ ሲባክን ይታያል…
ሹለክ በከፍተኛ ጥንቃቄ ላይ ነው፡፡ የደምሴን ኮቴ በቅርብ እርቀት እየተከተለ ነው… ደምሴ፣ ወደ አሮጌው አውቶብስ ገባ፡፡ ከዱበርቲዋ ጎረቤቱ ጋር እያወጋ፣ ካጠገባቸው ተቀመጠ፡፡ ሹለክ ከጎኑ ቆሞ ሲመለከተው፣ ደምሴ ወደ ዱበርቲዋ ተጠጋ። አውቶብሱም ወደ ደሴ መጓዝ ጀመረ፤ ሹለክም ሥራውን … ጀመረ፡፡ የተጋሩት ወንበር፣ ሦስቱንም የልማድ እስረኞች ያነጋግራቸው ጀምሯል- እየቆየም ያግባባቸው ይሆናል፡፡
ሹለከም አውቶብሱም ለ“ቢዝነሣቸው” እየፈጠኑ ነው… ሕይወት በሴኮንዶች ክፍልፋይ ልትመተር ተዘጋጀች… ሹለክ እጁን ከደምሴ ትከሻ ላይ አደረገ፡፡ ልቡ በትንሹ ትርትር ማለት ጀመረች። ኪሥ በማውለቅ የተካኑት ጣቶቹ ስለታቸውን አፋጩ፡፡
“… ለገጠመኝ አተካሮ ብዬ እንጅ ነው የግራውን ጥማድ በሬዬን ነጥዬ የሸጥኩት!... ሽማግሎች፣ ልጅህ ጠልፎ የህጣኗን ህግ ስላበላሸ… ሠርግ ደግሠህ ወዳጅ ዘመድ መካስ አለብህ … ካለበለዚያ ዴም እንዳትቃባ ሲለኝ!...” አለ ደምሴ ከዱበርቲዋ እየተቀበለ በጉንጩ የወጠረውን ጫት በምላሱ እያማሰለ፡፡
“ህፃኗን ደፍሮ!?” ሹለክ በድንገት ጠየቀ፣ ዝም ከምል ብሎ፡፡
“ምን ይዴፍራል! ጠልፎ ሉያገባ ብል እንጂ! ነገር ሲያጣምሙይ ያስራ ሁለት ዓመት ሴት ህጣን ሁና ነው?” አለ ደምሴ፤ የካሣ ክፍያው ነገር እያናደደው፡፡
“አይዞ! ዱአ ነው ዋናው!... ትንሽ ዴም አፍሰህ ዱአ ይደረጋል!” አለ ዱበርቲዋ፣ ለሙሽራው ድንጋይ አድባር ቡና ማፍያ የገዟትን ጀበና እየደባበሱ፡፡ “አሁንም ያን ቅቤ ሙሽራውን ድንጋይ ቀባ ቀባ አርገህ ተለማምነህ ሂድ… እኔም ማምሻውን መንደርተኛውን ሰብስቤ ቡን አፈላለሁ…” አሉ ዱበርቲዋ ጀበናውን ለደምሴ እያቀበሉ፡፡
አውቶብሱ እየከነፈ ነው … ሹለከ ግን እስከ አሁን አልተሳካለትም፡፡ ዓላማው ግቡን ሳይመታ ደምሴ መውረጃው እየደረሰ ነው፡፡ ሹለክ፣ የሰውነቱን ሙለ ክብደት ከደምሴ ትከሻ ሊይ አሳረፈ፡፡ ደምሴም ከዱበርቲዋ ጋር ወሬውን ይኮመኩማል፡፡ ሹለክ ጣቶቹን ወደ ደምሴ ደረት ኪሥ አስጠጋ፡፡ ዘወርወር ብል ተጓዡን ቃኘ፡፡ በደምሴ ልጅ አስገድዶ መድፈርና በዱበርቲዋ ገድል ዙሪያ የሚወሩት ወጐች ይበልጥ ደርተዋል… ዱበረቲዋ ስለታምራቸው ሲነገር፣ በጫት ጉንጫቸውን እንደ ጐረምሳ ጉርሻ ወጥረው፣ ዐይናቸውን ፈጠጥ አድርገው ተጓዡን ይገላምጣሉ - በኩራት፡፡ ከእርሳቸው የበለጠ ታምረኛን፣ በመቼም ጊዜ በየትም ቦታ የመነተፈውን ይዞ ሹልክ ማለት የማይሳነውን የ“ሹለክ”ን ዝና የሚናገርለት ወይም የሚናገርበት ስለላለ፣ የልማድ ቧጋቿ ዱበርቲ ቢኩራሩ አይደንቅም- ይኩራሩ …
ሹለክ አሁን ልቡ በፍጥነት እየመታ ነው። ክንዱን ከአውቶብስ ወንበር መደገፊያ ሊይ ጣል አድርጐ እጁን ወደታች ላከ፡፡ ቀጫጭን ጣቶቹ ሲጋራ ብቻ ሳይሆን የደምሴን የኪስ አዝራር መያዝ ችለዋል፡፡ ችግራቸው ኪሱን መክፈት ላይ ነው። አውቶብሱም ፍጥነቱን ሥለጨመረ፣ ኮረኮንቹ መንገድ ገበጣ እያጫወተው ነው፡፡ አውቶብሱ ወደ ላይ ጉኖ ሲፈርጥ፣ ሲጠባበቅ የነበረው ሹለክ የደምሴን የደረት ኪስ ቁልፍ ከፈተ፡፡ 3
ደምሴ ወሬውን ቀጥሏል… ሹለክ ተጓዡን ዘወርወር ብል ከቃኘ በኋላ፣ የተማሩ ጣቶቹን ወደ ወርቁ ጉድጓድ ጨመራቸው፡፡ መቀሦቹ ያልሰራበትን መክሊት አፍሰው ወጡ… ደምሴ በሬ ሸጦ ኪሱ ውስጥ ያስቀመጠው 3 ሺህ ብር ከመቅፅበት በሰው እጅ መግባቱን አላወቀም፡፡ አውቶብሱ ቦሩ ሜዳ ሉደርስ ስለሆነ፣ ረዳቱ ትኬት መቀበል ጀምሯል፡፡
ሹለክ ወደ ኪሱ ከጨመራቸው የመቶ ብር ኖቶች ጋር ትኬት እንዳለ አረጋገጠ፡፡ የደምሴ ትኬት፣ እንደ ድርጭት በድንገት ቢያስደነግጠውም መሊ አላጣለትም፤ እጥፍጥፍ አድርጐ በመስኮቱ ወደ ውጭ ወረወረው! … ልቡ ግን እንደ ነጋሪት ይደልቅ ይዟል …
“ትኬት!” አለ እረዳቱ፡፡
ሹለክ ቀልጠፍ ብሎ ሰጠ፡፡ ደምሴ ግን “እህ!” ብል ተደሰቀ እንጅ፣ እጁን አልዘረጋም… ዱበርቲዋ እንደሰጡ የደምሴ ልብ ቀጥ ያለ መሰለ፡፡ የያዘውን ጀበና ለባለቤቲቱ መልሶ ከተቀመጠበት በድንገት ቆመ፡፡ ሹለክ ምንም ነገር እንዳልተከሰተ ተረጋግቶ፣ በተሰነጠቀው መስታወት ውጭ ውጩን ያያል። ደምሴ ደረቱን በሁለት እጁ እየዳሰሰ “ኧረ ጉድ ሆንኩ!” አለ ወደ ዱበርቲዋ ዞሮ፡፡
አላመነም፡፡
ጐንበስ ብል የወንበሩን ሥር ቃኘ፡፡
“ትኬቱ ጠፋህ?” አለ ሹለክ የሚደልቀውን ልቡን እየሸነገለ፡፡
“ብሬ ሁላ ጠፋይ!... ኧረ ጉድ! እሪ … እሪ!”
አሁን ደምሴ አመረረ… ተሳፋሪው ሁላ ተደናገጠ፡፡ ዱበርቲዋ፣ “የበሬህ ብር ሁሉ!? … እሪ!” በማለት አዳነቁት፡፡ ሹፌሩ አውቶብሱን አቁሞ እረዳቱን ጠየቀ፡፡
“ጋቢህን አራግፈህ እይ?... መቀመጫህንም፡፡” በማለት ሁለም በየአፉ ይናገራል፡፡
“ወይኔ ልጆቼ! ጉድ ሆንኩ ጐበዝ!... እሪ! ውይ ውይ!”
ደምሴ ጉንጮቹን ፈርክሰው መሃል ለመሃል የሚጐርፉ እንባዎቹን ለመጥረግ፣ ፊቱን ሞፈር በተጠየፈው እጁ ሞዠረው፡፡ ሰውነቱ በላብ ተጠመቀ፡፡ ወደ ፊት ወንበሮች ተንገዳግዶ እየሄደ ለቅሦውን ያስነካው ጀመረ፡፡
የቦሩ ሜዳ ወራጆች አውቶብሱን እንዲያስቆምላቸው ረዳቱን ተማፀኑ፡፡
“ልክ ነው!... እዛ ነው የወሰዱበት …” አለ፣ ሹለክ አፉ ላይ የመጣለትን፡፡ 4 አውቶብሱ ከቅድሙ የበለጠ እየከነፈ ነው፡፡ ሹፌሩ አንድ ነገር አውቋል… መንገድ ላይ ወራጅ እንዳለ ቢረዳም፣ አውቶብሱን ለማቆም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
“የት ነው የሚወስደን? … ተፈትሸንም ቢሆን እንውረድ!” እያለ ተሳፋሪው ይንጫጫል፡፡ ሹፌሩ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብል ወደ ፊት ሸመጠጠ፡፡
“ጐበዝ በቃ ያለንን እንርዳው!” አለ፣ ሹለክ ከኪሱ 50 ብር አውጥቶ እያንቀረፈፈ፡፡ የቀረችው 10 ብር ብቻ እንደሆነች አላጣውም… አሁን ሹፌሩን ማንም አላሰተዋለውም እንጂ፣ ሹለክን አሽሟጦታል። ዱበርቱዋም ደንግጠው ኩምሽሽ እንዳለ ነው… ምርቃናቸው ተገፏል፡፡
ሹለክ ከፊት ወንበር አካባቢ ካለ ሰዎች የተሰጠ ገንዘብ ለመቀበል ወደ ፊት ሲያመራ፣ ከሹፌሩ ጋር ዐይን ላይን ተጋጩ፡፡ ሹለክ በጣም ደነገጠ … የሹፌሩ መልከ አዲሱ አይደለም… ሹፌሩ ዘወር ብል ገላመጠው፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ነው፡፡ ሹለክ መደበኛ ሥራውን ለማከናወን ወደ ባቲ ሄዷል፡፡ ሲመለስ፣ ከአንድ የአፋር ቋንቋ ተናጋሪ ጋር በአንድ ወንበር ተቀምጦ ይጨዋወታል… ኮንቦልቻ ላይ አዲስ ተሳፋሪዎችን ሊጭን አውቶብሱ ቆመ፡፡ ከሹፌሩ ጥግ ከሞተሩ ኮፈን ላይ ሻንጣቸውን የጫኑ መንገደኞች እቃ ለመግዛት ወረዱ፤ ሹፌሩም ወረደ …
“ያን ሻንጣዬን ጠብቅ! እሺ?” አለ ሹለክ የመንገድ ጓደኛውን፡፡ ወዲያው መለስ ይልና፣ “አይ! … ለካ ብሬ ሁለ ሻንጣዬ ውስጥ ነው … መኪናው እንዳይሄድብኝ … ስመጣ እሰጥሃለሁ፡፡ እቃ የምገዛበት ሃምሳ ብር ሥጠኝ …” ብል ይጠይቀዋል፡፡
“ዝርዝር የለም!... ይሄ ነው ያለው” ብል መቶ ብር አውጥቶ ሰጠው፡፡ ከእቅድ በላይ የሠራው ሹለክ መቶ ብሩን እንደያዘ ወዲያው ሹልክ አለ። አውቶብሱ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ሹለክ ግን አልመጣም - አይመጣምም…
“ሹፌር!... እዚህ ሰው አለ! … እቃ ጠብቅ ብሏል” አለ አፋርኛ ተናጋሪው ጣቱን ሞተሩ ላይ ወዳለው ሻንጣ ቀስሮ፡፡
“ይሄማ እቃ የኛ ነው!” አሉ ባለቤቶቹ፡፡
“እቃ እኔ ነው ጠብቅ ብል … መቶ ብር ከሱ ወሰደ” አለ፣ አፋሩ ኪሱን እያመለከተ፡፡ ወዲያው፣ ሹለክ አጭበርብሮ እንደጠፋ ታወቀ፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ የነበረው ሾፌር፣ የዛሬው አውቶብስ ሾፌር ነው… አሁን ሹለክ ያሰባሰበውን 144 ብር ለደምሴ አስረከበ፡፡ ሹፌሩ እያከነፈ ያመጣውን አውቶብስ ደሴ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ በር ላይ 5
ገተረውና ወረደ፡፡ ሹለክ በጣም ደነገጠ… ሁሉም ነገር አሁን ገብቶታል፡፡ ፖሊሶች አውቶብሱን ከበቡ፡፡ ሁለቱ የፊት በሩን አስከፍተው ገቡ፡፡
“ይሄ ነው!” አለ ሹፌሩ፡፡ ደምሴ ፖሊሦችን ሲያይ፣ እሪታውን ጀመረ፡፡ ሹለክ በጣም ደንግጧል፡፡ ቀዝቃዛ ልብ በጀርባው እየፈለቀ ነው፡፡
“የት ጋ ነበረ የተቀመጠው?” ብሎ ፖሊሱ ሲጠይቅ፣ ሹለክ ተሽቀዳድሞ “እዚህ ነው!” በማለት ጠቆመ፡፡ ሁለም በያፉ ተልጐመጐመ፡፡
“አሁን ሁላችሁም እየተፈተሻችሁ ትወርዳላችሁ፡፡” አለ መቶ አለቃ፡፡
ሹለክ አንዳች ነገር ሆድ ዕቃውን አንጓጓው፤ ልቡ ሊፈነዳ እንደቀረበ ፊኛ ተወጠረ፡፡ ሰውነቱም ያለቅጥ መራድ ጀመረ፡፡ ፍርሀት ሆዱ ውስጥ ገብቶ፣ እንደ ቅቤ መግፊያ ቅል መናጡን ተያያዘው፤ ማንም ሰው ግን አላስተዋለውም፡፡
“በዚህኛው እረድፍ ያላችሁ ቀጥሉ!”
በእነ ሹለክ ረድፍ ያለው ተሳፋሪ ተነሳ፡፡ በሚቀጥሉት ወንበር ላይ ያሉትም መንገደኞች እየተነሱ፣ ፍተሻው ቀጥሏል፡፡ ሹለክ መውጫ ቀዳዳ ጠፋው፡፡ ፖሊሦችም እሱን መጠርጠራቸው እና በጥብቅ መፈተሻቸው አይቀርም፡፡ ልቡ ፈንድቶ፣ ሥራውን ሊያቆም ነው … መቶ አለቃው ሁሉንም እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ይመስላል፡፡
“ቀልጠፍ ቀልጠፍ ብላችሁ ተነሱ እንጅ ጐበዝ!” አለ፣ ፈታሹ ፖሊስ፡፡ ከእነ ሹለክ ወንበር ፊት ያሉት መንገደኞች ተሽቀዳድመው ተነሱ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሹለክ መሽሎኪያ አጣ፡፡ ተፋፋው እንደ ሸክላ ሰሀን ከፊቱ ሊይ ተከሰከሰ… ከጭንቀቱ የተነሳ አንዳች ነገር ሊተነፍስ፣ ‘ይሄው ብሩ እዚህ ወድቋል!’ ሉል አሰበ… መሽሎኪያ ቢሆነው፡፡
ሹለክ፣ በድንገት አንዳች መሽሎኪያ ብልጭ አለለት፡፡ የተጠቀለሉትን ኖቶች ከኪሱ ውሰጥ ከፈለጋቸው በኋላ፣ የዱበርቲዋን ዓይን ቃኘ - በርበሩን ያያሉ፡፡ ጣቶቹ፣ የሦስት ሺህ ብር ኖቶች ይዘው በድንገት ከኪሱ ወጡ … ኖቶቹን ጠቀለለና በለሆሳስ ከዱበርቲዋ ጀበና ውስጥ ከተተው … ሥራውን ለማቆም የሴኮንድ ክፍልፋይ የቀሩት የሚመስለው መለኛ ልቡ፣ አሁን በደስታ ባይቦርቅም ትንሽ ተንፈስ አለ፡፡
“በሉ ተነሱ እስኪ!” ብሎ መቶ አለቀ የነሹለክን ወንበር በትኩረት ለመቃኘት ሞከረ፡፡ ሹለክንም በጥንቃቄ መፈተሻቸውን ተያያዙት፡፡ ከኃላፊያቸው ምልክት የተሰጣቸው ፖሊሦች፣ ወደ ጣቢያው አስገቡትና ፓንቱን ሳይቀር አስወለቁት፡፡ ሹለክ ግን ከአስር ብር ውጭ አምስት ሳንቲም አልተገኘበትም፡፡
“ምነው እኔን በተለየ ሁኔታ ፈተሻችሁኝሣ” ሊል አስቦ ነበረ፡፡ በኋሊ ግን ጐመን በጤና ማለትን መርጦ ፍተሻውን እንደጨረሰ በፍጥነት ወጣ… ቀልቡ ያለው የመቶ ብር ኖቶችን ከደበቀው የዱበርቲዋ ጀበና ላይ ነው፡፡ 6 ደምሴን የሚጠባበቁት ዱበርቲ፣ ከጣቢያው አለፍ ብል ከሚገኘው ፅድ ሥር ቆመዋል፡፡ ፖሊስ ጣቢያው በር ሊይ ዱበርቲዋን ሲያጣቸው በሀዘን መሰበር የጀመረው ልቡ፣ በርቀት እስከ ጀበናቸው ሲያያቸው በደስታ መጠገግ ጀመረ፡፡ ፈገግታ እያሳያቸው ቀረብ ሲል፣ “አንተን ዴሞ ምን አርግ ብለው ነው ወደ ውስጥ የጠሩህ ልጄ?” ብለው ሳይጨርሱት - “ብር አዋጥቼና አሰባስቤ በመስጠቴ አድናቆታቸውን እየገለፁልኝ ነው!” አላቸው- ጮላው፡፡
“ዴግ ሥራ ጥሩ ነው ልጄ! ካሊህ ታገኘዋለህ!”
“አዎ! እስዎም’ኮ ጥሩ ሰው ነውሁ… እናቴን ነው የሚመስልሁ!”
“አይ ልጄ! እናትህ አሉ?”
“አለች! እንደውም እንደስዎ ባለ ውቃቢ ናት!... እቺን ጀበና ስንት ገዙት! ጀበናዋ ሲሰበር ዛሯ ተነስቶ የቤቱን ሰው ሁላ ካልፈጀሁ ብል ነበር…” በማለት አስተዛዝኖ ጠየቃቸው- በወሎ ዘዬው፡፡
“ኧረ ቀላል ነው! ዴሞ ለዚህ ተጨነቅህ ሁለት ብር ነው” አለት ወደ ዘረጋላቸው እጁ ጀበናውን እያስተላለፉ…
“ቆንጆ ጀበና ናት!... እንደው እናቴ ካልደፈርኩህ… ላንቱም የቡና መግዣ ይሆንኋል… ለእኔ ሽጡልኝ፤ ደሞም ይመርቁኛል!” በማለት 10 ብር አውጥቶ አስጨበጣቸው፤ ዱበርቲዋ ደነገጡ፡፡ 2 ብር በገዙት ጀበና 8 ብር ማትረፍ አይታመንም … ደስታቸው ከፊታቸው ላይ እንደ ፈንዲሻ ቆል ይዘገናል፡፡
“አይ ልጄ! አላህ ይሰጥሀል! እናለሞቼ ይጠብቁህ…” ብለው መርቀው ሳይጨርሱ፣ አዲስ ሀሳብ ብልጭ አለባቸው፡ ሴቷ ዛራቸው ራሄል፣ ለሙሽራው ድንጋይ መከደሚያ እንዲገዙ የታዘዙትን በመሸጣቸው እንዳትጣላቸው ሰጉ፡ “ደግሜ እገዛው የለ!” በማለት ተፅናኑና ከሹለክ ጋር ተሰነባብተው ሄዱ… ወዲያው ደግሞ ልባቸው አመነታ፡፡
ወጣቱም፣ አዛውንቷም በአንድ ጉዳይ አንድ ናቸው፤ ሁለቱም የልማድ እስረኞች ናቸው፤ ሁለቱም በአንድ ዘመን የሚነፍስ፣ ሥልጡን ሽውታ ያልነካው፣ የንፋስ ወጀብ የሚያንከላውሳቸው የመንፈስ መጢቃ ናቸው። በጋራ የቆሙለት ልማድ፣ በተቃራኒ ያቆማቸዋል… በልማድ የታሰረ የሀበሻ ሕሉና ደግሞ፣ በትንሽ የማሟሻ እሳት እንደሚፈረካከስ ረጋ ሠራሽ ምጣድ ጽናት ይጎለዋል፤ የቆመለትም የቆመበትም “መርሁ” የሚገዛው፣ ከማይሰማ ምጣዱ ተፈቅፍቆ በወጣ “እንጀራው” ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ ሀበሻ “በእንጀራዬ አትምጣብኝ ካለ …” አመረረ ማለት ነው የሚባለው …
አዛውንቷም የልማድ እስረኛ፣ ሆድና ልማድ በቁም እየተገጫጩ ሲያሸብሯቸው ሕሊናቸው መፈረካከስ ጀመረ- እንደ ረጋ ሠራሽ ሸክላ…  
ሹለክ ግን የሠራ አካላቱ ጥርስ ብቻ ሆኗል፡፡ ጀበናው ውስጥ የደበቀውን መክሊት ለማውጣት ጀበናውን በአፉ ዘቅዝቆ ቂጡን ቢጠበጥበውም ጠቅልል ያስገባው የብር ኖት ግን በቀላሉ ሊወጣ አልፈለገም፤ ውስጥ እንደ ገባ ስለ ተዘረጋም፣ የጀበናው አንገት ሊያስወጣው አልቻለም፡፡
ደገር ሄደው ሣለ የከላላው ሼህ፣ “ዴሞ ልሙሽራው ድንጋይ ገብሪ! እምቢ ካልሽ ዋ! ራሄል ቀልድ አታውቅም። ሰነካክላ ነው የምታስቀምጥሽ!” የተባሉት በእዝነ ሕሊናቸው ታወሳቸው፡፡ ከብብታቸው የሸጐጡትን 10 ብር መዥርጠው እያወጡ፣ “ማነህ! የኔ ልጅ …” እያሉ ወደ ሹለክ ሮጡ፡፡
“እህህ! አንቀጠቀጠኝ ልጄ! ... በራሄል ቀልድ የለም! እንዴምትጣሊኝ ትከሻዬ ነገረኝ … እንካ!” ብለው 10 ብሩን በቀኝ እጃቸው አንቀርፍፈው፣ በግራ እጃቸው ጀበናቸውን ለቀም አደረጉ፡፡ ሹለክ ሰፈሩ ሲደርስ ጀበናውን ሰብሮ ብሩን ለማውጣት ቢወስንም፣ እስከ አሁንም እየታገለ ነበርና፡፡ ዱበርቲዋ ግን፣ በጣም ስለጓጓለት በቀላሉ እንደማይሰጣቸው ገምተዋል፡፡
“እንዴ!... አንድዬ ሸጠውልኝ!... ካነሥዎት ወደዛ እንሂድና ብር ልጨምርልሁ!” አላቸው ለደምሴ 50 ብር በማዋጣቱ የኪሱ ባዶነት እየታወሰው፡፡ ዱበርቲዋ ጀበናቸውን በሁለት እጃቸው ግጥም አድርገው ይዘው እንዲለቅላቸው ተማፀኑ … ሹለክ ምሊጩ እንደተነካ ጓንዴ አባረቀ፤ “የተሸጠ አይመለስም!”
የልማድ ምርኮኞቹ ሥለ ልማዳቸው ሊዋደቁ ሙግት ገጠሙ… የቃላት ሰይፍ ተማዘዙ፡፡ “ከፈለጉ ብር ልጨምርልሁ እንጂ …” በማለት ሹለክ ያሰበውን ሁሉ ተናግሮ ሳይጨርስ፣ የውቃቢያቸውን ቅጣት የፈሩት ዱበርቲ፣ ጃኬቱን ሞጭጨው ይዘው ጮሁ፡፡ ከጣቢያው በር ላይ ሆኖ ሲያያቸው የነበረው ፖሊስ፣ ጩኸቱን እንደ ሰማ አንገቱን ወደ አለቃው ቢሮ አዞረ… በነ ሹለክ አጠገብ ሢያልፍ የነበረ አንድ መንገደኛ ወጣት፣ ወደ እነሱ አቅጣጫ ራመድ ራመድ አለ- የሆድና የልማድ እስረኞችን ሙግት ሊዳኝ፡፡
“ጀበናዬን አምጣ ብያለሁ! እንካ ብርህን!” ብለው ብሩን ወደ ኪሱ ከተው ጀበናቸውን በኃይል መንጭቀው ሊቀሙ ሲታገለ፣ “ወንጀለኛው” ጀበና አስፋልቱ ጠርዝ ላይ ተከሰከሰ፡፡ ተጠቅልለው ጀበናው ሆድ ውስጥ የተቀበሩት የመቶ ብር ቅጠሎች፣ እንደተነከረ ሥጋጃ አስፋልቱ ላይ ተሰጡ… አዙሮ የማያየው የጀበናው አንገት ብቻ አልደቀቀም፡፡
“እሪ … ያላለህ!”
ዱበርቲዋ እንደ ልጥ ሚስት ሐውልት ሆነው ቀሩ፡፡ ሹለክ ለመሮጥ እግሩን ሲያነሳ መንገደኛው ወጣት ጃኬቱን ጨምድዶ አቆመው…

Published in ልብ-ወለድ

“ሁለት ጎረምሶች በሬዲዮ እያወሩ ነው፤ሁለት ጎረምሶች ያልኩበት ምክንያት ጋዜጠኞች ለማለት ስለከበደኝ/ስለተቸገርኩ ነው” የሚለው እያዩ ፈንገስ፤በተለይ በኤፍኤሞች ስለምናደምጣቸው ጋዜጠኞች ትዝብቱን ይነቅሳል፡፡ ተመልካቹም በፈገግታ ያጅበዋል፡፡ “ታዲያ ጎረምሶቹ የሚያወሩት ሩኒ ስለተባለ የእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግ ተጫዋች ነበር፡፡ እንደነሱ አገላለፅ፤ ሩኒ ለተከታታይ ስምንት ጨዋታዎች ጎል ባለማግባቱ ወደ አዕምሮ ህክምና ባለሙያ ዘንድ ሄደ፡፡ ዜናው ይሄ ነበር፡፡ ታዲያ እኔስ ምን አልኩ?… እናንተን ቀድሞአችሁ ሄደ?”
እንዲህ እንዲህ እያለና እያዋዛ ፈንገስ ተስፋፍቶባቸዋል ያላቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን በዋናነት ነቅሶ በጦቢያ የግጥም በጃዝ ወርሃዊ ፕሮግራም መሃል በማቅረብ የሚታወቀው እያዩ ፈንገስ፤ ይህን መሰሉን መነባንብ ማቅረብ የጀመረበትን አንደኛ ዓመት የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በብሄራዊ ቴአትር አክብሮአል፡፡
እያዩ ፈንገስ ማህበራዊ እንከኖቻችንን ሲነቅስ….እንዲህ ይለናል፤
 አንዱ ወደ አንድ ምግብ ቤት ገብቶ ቀይ ወጥ አዘዘና ከበላ በኋላ እጁን ለማስለቀቅ በውሃና በሳሙና ቢታገል ቢታገል እምቢኝ ይለዋል፡፡ ታዲያ ያን ጊዜ ወደ ምግብ ቤት ባለቤትዋ ዞር ብሎ “ሰማሽ እቱ…ወጡን የሰራሽው በእንሶስላ ነው እንዴ?” ብሎአት እርፍ፡፡
እያዩ ፈንገስ?
ሶስት ዓመታት ያለፉት የጦቢያ ግጥም በጃዝ ፕሮግራም፤ ከዕለት ወደ ዕለት ተወዳጅነቱ እየጨመረና የአቀራረብ ለዛውም እየተሻሻለ በመምጣት ላይ ነው። መድረኩ ከዛሬ አንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ በተወዳጁ ገጣሚ በረከት በላይነህ ፀሃፊነትና በተዋናይ ግሩም ዘነበ ድንቅ አተዋወን የመድረክ መነባንብ ማቅረብ ጀምሮአል። እያዩ ፈንገስ የተባለው መምህርና ገጣሚ ገፀ-ባህሪ “በአገራችን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስንክሳሮች እየበዙና እየተባዙ ፈንገስ እያመጡ ሄደዋል። ፈንገሱም ወደ ሁላችንም ቤት እየተዛመተ ነው” የሚል ፍልስፍና ያለው አዕምሮው የተነካ ገፀ ባህሪ ነው፡፡ በየወሩ በልዩ-ልዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩትን ትዝብቱን አዝናኝ በሆነ መልኩ የሚያቀርብበት መድረክ ነው የእያዩ ፈንገስ ዝግጅት፡፡ እያዩ ሲያሻው ጠፋብኝ ብሎ ከሚነግረን ባለ ቀይ ሽፋን አጀንዳው ላይ ከተፃፉት ግጥሞቹ በወዳጁ ነፋስ አማካኝነት ውስጠ ወይራ ግጥሞችን ያስኮመኩመናል። ሲሻው ደግሞ በሳቅ እያፈረሰ ልካችንን ይነግረናል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ በአንዳች ትራጀዲ ውስጥ ገብቶ ስሜትን ሰቅዞ የሚይዝ ዲስኩር ያሰማል፡፡ እንዲህ የሰውን ስሜት እላይና እታች እያደረሰ ላለፉት 12 ወራት ዝግጅቱን ሳያቋርጥ ያቀረበው እያዩ ፈንገስ ነው እንግዲህ አንደኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ በብሄራዊ ቴአትር ለተጋባዥ እንግዶች ልዩ ዝግጅቱን ያቀረበው፡፡
አንዱ አለን እያዩ ፈንገስ፤ወደ መብራት ሃይል ይደውልና ሄሎ መብራት ሃይል ነው? እንዲያው ምነው ባካችሁ ምን አድርገናችሁ ነው----እንዲህ ሶስት ቀናት ሙሉ በተከታታይ መብራት ያበራችሁልን?...ነውር አይደለም እንዴ? ነው ወይስ መብራት አጥፊው ስልጠና ገብቶ ነው? ይሄ ከእናንተ አይጠበቅም፡፡ ስራችሁን ባግባቡ መስራት አለባችሁ፡፡ ሦስት ቀን ሙሉ መብራት ትሰጡናላችሁ እንዴ? ……. እንዲህ እያለ የሳቅ መተንፈሻ ይፈጥርልናል፡፡
ግሩም ዘነበ?
ካወቅሁት ረዘም ያለ ጊዜን ያስቆጠረው ግሩም ዘነበ፤ በየጊዜው ራሱን በጥበቡ ዓለም እያሳደገ ሳይሰለችና በመድረክ ላይ ችክ ሳይል የተመልካችን ስሜት እንደተቆጣጠረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ግሩሜ ሲያሻው በመድረክ ቴአትር እንደ ለዕረፍት የመጣ ፍቅር፣ ቤቱ፣ ንጉስ አርማህ ፣ ፍቅር የተራበ ወዘተ--- ሲያሻው በሬዲዮ ጋዜጠኝነት፣ ሲያሻው በበጎ አድራጎት ስራ ላይ በመሰማራት መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በየዩኒቨርሲቲው በመዞር ልምዱን የሚያካፍልና አዝናንቶ አስተምሮ የሚመለስ፣ ሲያሻው በጦቢያ ግጥም በጃዝ ፕሮግራም ላይ በግጥም አቅራቢነት፣ በመድረክ መሪነት፣ በመነባንብ አቅራቢነትና አሁን ደግሞ ተለይቶ በታወቀበት በእያዩ ፈንገስ ልዩ አቀራረብ ከአድማጭ ተመልካቹ ጋር አብሮ አለ፡፡ ግሩሜ በሜጋ አንፊ ቴአትር በነበረበት ወቅት የተዋጣለት የህፃናት ቴአትር ሰርቶ እንደነበርም አስታውሳለሁ፡፡
የዛሬ ሳምንቱ የብሔራዊው ፕሮግራም በተወዳጁ ገጣሚ አበባው መላኩ የመድረክ አጋፋሪነት (ከጥሩ ባህላዊ አለባበስ ጋር) የተመራ ሲሆን በቅድሚያ ንግግር እንዲያደርግ የተጋበዘው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነበር፡፡ ዳንኤል የእያዩ ፈንገስን የአንድ ዓመት መነባንብ አቀራረብ ከነባራዊ ህይወታችን ጋር እያስተሳሰረ ማራኪ ንግግር በመድረኩ ላይ አቅርቧል፡፡ እስቲ ከተናገረው ውስጥ ጥቂቱን ልጥቀስላችሁ፡፡
በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብና የድርሰት ዓለም ውስጥ እያዩ ፈንገስን የመሳሰሉት ገፀ-ባህሪያት አልፎ-አልፎ ብቅ የሚሉ ቢሆንም አዲሶቻችን አይደሉም፡፡ በ“ፍቅር እስከመቃብር” ላይ የምናገኘው ጉዱ ካሳ እንዲሁም በአፈ-ታሪክ የምናውቃቸው አለቃ ገብረሃና ለእዚህ ማሳያ ይሆናሉ፡፡ እነኚህን የመሳሰሉ ገፀ-ባህሪያት በመንግስት ፖለቲካ፣ በማህበራዊና በባህል ጉዳዮች ወይም በሌሎች ርዕሶች ዙሪያ የህብረተሰቡን ችግሮች መዘው በማውጣት ሲሞግቱ የኖሩ ናቸው፡፡ አዝማሪዎችም ቢሆኑ በበርካታ ግጥሞቻቸው የየዘመናቸውን ፖለቲካና አገዛዝ አጣጥለውበታል፡፡
ወደ ዕውነታው ዓለም ስንመለስ ደግሞ የአፄ ቴዎድሮስ ሚስት ምንትዋብ መቅደላ ድረስ እየተከታተለች አፄውን በስድብ ቁም ስቅላቸውን ስታሳያቸው እንደነበር ዳንኤል አስታውሶ፣ አፄ ቴዎድሮስ በወቅቱ ያሳዩትን ትዕግስት ከልብ አድንቆአል፡፡ ለአሁን መሪዎቻችንም የአፄ ቴዎድሮስን ሰምቶ ቻይነት ትዕግስት እንዲሰጥልን ምኞቱን አቅርቦአል፡፡ አገርን በሪፖርት እንደማወቅ ከባድ ነገር የለም ያለው ዳንኤል፤ መንግስት ሆደ ሰፊ በመሆን በሪፖርት ከሚቀርብለት ፅሁፍ ባሻገር የድሮ ነገስታት እረኛ ምን አለ እንዲሉ ከራሱ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ድምፅ ሊያደምጥ ይገባል የሚል አስተያየቱን ሰጥቶአል፡፡
እያዩ ፈንገስ ካጫወተን አንዳንድ ነጥቦችን እንጨምር፡
ማህበራዊ ችግሮቻችን እየባሱ ሰው በኑሮ ውድነት እየደቀቀ ነው የመጣው የሚለው እያዩ፤ የአንዳንዱን ሰው መደንዘዝ ሲናገር፤ አንዳንዱ ሰው ራሱ ደውሎ ራሱ ስልኩን ለማንሳት ሁሉ ይዳዳዋል ይለናል፡፡ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አካባቢ ሴተኛ አዳሪዎች ለተማሪዎች የዱቤ አገልግሎት ጀምረናል የሚል ማስታወቂያ ለጥፈው በዓይኔ አይቻለሁ እያለ በትዝብት ጅራፍ ይገርፈናል፡፡ ከራሳቸው አዲስ ጅንስ ሱሪ ጋር እንኳን ገና ያልተለማመዱ የሲኖትራክ መኪና ጎረምሳ ሾፌሮች ህዝቡን ጨረሱት ይለናል፡፡
በርካታ ጋዜጦችና መፅሄቶች በተዘጉበት በአሁኑ ወቅት አገራዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ግጥሞች የሚቀርቡበት መድረክ አለማጣት ተመስገን የሚያሰኝ ነው፡፡ ለነገሩ ሰዎች በአዳራሽ ተሰብስበው ግጥም ስላዳመጡና ትንፋሽ ስለተለዋወጡ መንግስትን የሚጎዳው አንዳችም ነገር አለ ብዬ አላስብም፡፡ ኪነት ስራዋ የህዝብን ስሜት ማንፀባረቅ ነውና ሲሆን ሲሆን ህዝቡ ምን ይላል የሚለውን የማወቂያ አንዱ መንገድ አድርጎ መውሰድ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ብሔራዊ ቴአትርም አዳራሹን ሊያውም በቅዳሜ ቀን መፍቀዱ የሚያስመሰግነው ነው፡፡
ፕሮግራሙ እንደ ወትሮው ሁሉ ሰዓት አክብሮ አልጀመረም፡፡ ይህ ከጦቢያ ግጥምን በጃዝ ፕሮግራም የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ተመልካቹም ወደ አዳራሹ ቀድሞ ገብቶ “ሰው አለ” በማለት አራት አምስት ወንበር የመያዙን ራስ ወዳድነት ማቆም አለበት፡፡ ማህበራዊ ህፀፆችን እየነቀሰ የሚያሰማን እያዩም በ “ሰው አለ” ጉዳይ አንዳች ነገር ሊለን ይገባል፡፡
ሌላው በዚህ ፕሮግራም ያየሁትና ትንሽ ግራ ያጋባኝ ነገር የፕሮግራሙ ዋና ስፖንሰር በደሌ ቢራ ፖስተር አሰቃቀል ነው፡፡ ማህበራዊ ህፀፆች እየተነቀሱ በሚወጡበት መድረክ ወጣቱን ወደ አንድ ዓይነት ዓለም እየወሰደው ያለው የአልኮል መጠጥ በዚያ ደረጃ መድረኩን ሞልቶ ገዝፎ ሲወጣ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በደሌ ስፖንሰር ቢያደርግም ማስታወቂያው እንዲያ በተጋነነ መልኩ ሊሰቀልለት ይገባል የሚል ዕምነት የለኝም። ለመድረኩም ክብር መስጠት ይኖርብናል፡፡ ቸር ያሰንብተን!

Published in ጥበብ

(ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ)
ከጌዴዎን ግምጃ
         በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሥር ከተደራጀ ፬ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ከየካቲት 21 - የካቲት 22 ቀን 2007 ዓ.ም የቆየ ዐውደ ጥናት በደብረ ማርቆስ ቤተ መንግሥት የባህል አዳራሽ አካሂዶ ነበር፡፡ በጉባኤው ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራን የተገኙ ሲሆን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባልና ባለቅኔ አቶ ስማቸው ንጋቱም የዐውደ ጥናቱ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የቦርድ አባሉ አቶ ስማቸው ባለቅኔ ብቻ ሳይሆኑ የአማራ ክልል ገጠር መንገዶች ዋና ሥራ አስኪያጅም ናቸው፡፡
ተወልደው ያደጉት እንደ ቀድሞው አጠራር በደብረ ማርቆስ አውራጃ በቢቡኝ ወረዳ በተለይም ቢቡኝ ልጐ ጽዮን በተባለች ቦታ ነው፡፡ የትውልድ ቀናቸው 1952 ዓ.ም፡፡ ባለቅኔው ሥራ አስኪያጅ ከዘጋቢው ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዳስረዱት፤ በልጅነታቸው ፊደል የቆጠሩትና ውዳሴ ማርያም የተማሩት በወላጅ አባታቸው በሊቀ ካህናት ንጋቱ ዓለሙ አስተማሪነት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በአካባቢው ወደነበሩት ትምህርት ቤቶች በመሔድ መዝሙረ ዳዊት፣ ጾመ ድጓ፣ ከድጓ ደግሞ ዘመነ ዮሐንስ የሚባለውን የትምህርት ክፍል ከተማሩ በኋላ ወደ ቅኔ ቤት ተጉዘዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የሄዱበት ቅኔ ቤት ገደብ ጊዮርጊስ ይባላል፡፡ ገደብ ጊዮርጊስ በዚያው አካባቢ የሚገኝ ሲሆን የቅኔ መምህሩ ዐድምዑ ተስፋ ይባሉ ነበር፡፡ አቶ ስማቸው የቅኔ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደገና በበለጠ ለማለዘብ የጫቢ ማርያም የቅኔ መምህር ወደነበሩት መሪጌታ ወልዴ…ይሄዳሉ፡፡
መሪጌታ ወልዴ ኦሮሞና ወለጋ የሆሮጉድሩ ተወላጅ ሲሆኑ ቅኔ ለመማር ከወለጋ ወደ ጎጃም ተሻግረው ቅኔና ዜማ የተማሩና በዚያው በመምህርነት ተሰይመው ጫቢ ማርያም በርካታ ደቀመዛሙርትን ያፈሩ ታላቅ የቅኔ መምህር ናቸው፡፡ ባለቅኔው ሥራ አስኪያጅ ከዚህ በመቀጠል ከደንበጫ ከተማ በላይ ወደ ምትገኘው ደብረ ምጥማቅ ወደተባለች ቦታ በመጓዝ፣ ከመሪጌታ ይትባረክ ዘንድ በውስጠዘ መንገድ የቅኔ ሙያን አብስለው ተመርቀዋል፡፡ በዚሁ በቃኝ ያላሉት አቶ ስማቸው፤ ወደ ድንጋይ በር ሥላሴ ተጉዘው ከታላቁ የቅኔ መምህር ከግጨው መንክር ዘንድ የጎዳና፣ የምርምርና የቅጽል ተምሳሌ የቅኔ መንገዶችን ተምረዋል፡፡ የቅኔው ባለሙያ አቶ ስማቸው፤ ከድንጋይ በር ሥላሴ እንደገና ወደ ጫቢ ማርያም መሪጌታ ወልዴ ዘንድ ተመልሰው የቅኔ አስነጋሪ ሆነዋል፡፡ ከዚያም የሚያስተምሩዋቸውን የቅኔ ተማሪዎች በመያዝ ወደ ደብረ ኤልያስ ቅኔ ቤት ወርደዋል፡፡
ደብረ ኤልያስ በዘመኑ በጎዳናና በታሪክ የቅኔ መንገድ ከታወቁት ከመሪጌታ መሠረት አሥራቴ ዘንድ የጎዳናና የታሪክ የቅኔ መንገድን አመሣጥረውና አራቅቀው እዚያው ደብረ ኤልያስ አስነጋሪ ሆነዋል፡፡ ከዚያም የራሳቸውን ጉባኤ እንዲዘረጉ ተፈቅዶላቸው ራሳቸውን ችለው ለሦስት ዓመታት ያህል ቅኔ አስተምረዋል፡፡ አንዱን የዕውቀት ዘርፍ ሲጨብጡት ሌላውም ያማልላልና እንደገና የዘረጉትን ጉባኤ አጥፈው በጊዜው አባ መዘምር፣ በኋላ አቡነ ቶማስ ወደተባሉት በመሄድ ትርጓሜ መጻሕፍትን ተምረዋል፡፡ የአባ መዘምር ትርጓሜ መጻሕፍት ወንበር ይገኝ የነበረው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሲሆን በአጋጣሚ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የነሐሴ ተክለሃይማኖትን በዓለ ንግሥ ለማክበር ወደ ቦታው በመጡበት ጊዜ የዛሬው ሥራ አስኪያጅ የያኔው የትርጓሜ መጻሕፍት ተማሪ ስማቸው፤ 12 መወድስ ቅኔ ዘርፈው ለፓትርያርኩ ያበረክቷቸዋል፡፡
አቡነ ቴዎፍሎስም አስቀድመው ደብረኤልያስ የመሪጌታ መሠረት የቅኔ ተማሪ ስለነበሩና የቅኔውንም መንገድ ስለተረዱት፤ ተማሪ ስማቸውን፤ “አንተ የመሠረት ተማሪ ነህ እንዴ?” ብለው ይጠይቋቸል፡፡ አቶ ስማቸውም እራሳቸውን በመነቅነቅ የመሪጌታ መሠረት ደቀመዝሙር መሆናቸውን ያበሥራሉ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ አቶ ስማቸው ንጋቱ እድለኛ ሆኑና ፓትርያርኩ ከደብረሊባኖስ ወደ አዲስ አበባ ያመጡና በእርሳቸው ትእዛዝ ሰዋስወብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ አዳሪ ትምህርት ቤት ይገባሉ፡፡ በዚያም ዘመናዊ ትምህርት ይማራሉ፡፡ በወቅቱ ከ1ኛ-12ኛ የነበረውን የትምህርት ደረጃም በ6 ዓመት ያጠናቅቃሉ፡፡
ባለቅኔው ስማቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት በዲግሪ ይመረቃሉ፡፡ በ1975 ዓ.ም ደግሞ በኢትዮጵያ አስመጪና ላኪ ኮርፖሬሽን ተቀጥረው በተለያየ ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም ባለሙያ ሁሉ ወደ የተወለደበት ክልል ሄዶ መሥራት እንዳለበት የሚያስገነዝብ መመሪያ በመንግሥት በወጣበት ወቅት እርሳቸውም ወደ ባሕርዳር ሄደው በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በተለያየ ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡
በአገልግሎት ላይ እያሉም መንግሥት በሰጣቸው የትምህርት እድል ተጠቅመው በድርጅታዊ አመራር ሳይንስ በማስትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የአማራ ገጠር መንገዶች ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይም አቶ ስማቸው ሀገራቸውን በከፍተኛ የአመራር እርከን ለ32 ዓመት አገልግለዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ከዚህም በተጨማሪ ፤ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል ሆነው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ከሥራ አመራሩና ከቦርድ አባላት ጋር በመመካከር የሚሰጡት ውሳኔ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተመሰረተ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በጥሩ የዕድገት ጎዳና ላይ እንዲገኝ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ እኒህ ምሁር የሐዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም በአዘጋጀው ዐውደ ጥናት ላይ ሲናገሩ፤ “ሐዲስ ዓለማየሁ በተወለዱበት እንደዳም መንደር በእግሬ እንዳልተመላለስኩ ዛሬ በሠራነው የገጠር መንገድ መቶ ጊዜ መኪናዎች ይመላለሱበታል፡፡ ደበሎ ለብሼ በእግሬ ለቅኔ ትምህርት የተጓዝኩባቸው ቦታዎች በእኔም አስተዋጽኦ ጭምር ዛሬ በዘመናዊ የዐውራ ጎዳና መንገድ ተቀይረው ሳይ በእጅጉ እደሰታለሁ” ብለዋል፡፡ ከዚህም ተነሥተው የሚከተሉትን  ቅኔዎች ዘርፈዋል፡፡
ጉባኤ ቃና
ዘመነ አሪት ህልው ዘመነ ሐዲስ መነነ፡፡
ዘመነ ሐዲስ ብሉይ አምጣነ ኦሪተ ኮነ፡፡
ፍቺ፡- ነዋሪ የሆነው የኦሪት ዘመን ሐዲሱን ዘመን ናቀ፡፡
      አሮጌው የሐዲስ ዘመን ኦሪትን ሆኗልና፡፡
ምሥጢር፡- ጎጃም ውስጥ የኦሪት ባህልና ልማድ አለ፡፡ ጎጃም ውስጥ በሰንበት ውሃ አይቀዳም፡፡ አስቀድሞ የዐርብ ውሀ ይቀዳል፤ ከቦታ ቦታ አይሄድም፡፡ ቡና አይወቀጥም፣ የበግና የፍየል ደም መጠጣት የኦሪት ልማድ ነውና ይህ በጎጃም አለ፡፡ ሐዲስ አለማየሁ ኦሪት ሆነ ብለው የጎጃምን ባህል ሲያሳዩ ነው፡፡
ዘአምላኪየ
ገቢረ መንክራት ማርቆስ አመ ውስተ ሐቅል
ተሠርዓ፡፡
እህተ ሳሌም ጎርተ ሥላሴ ኀዘንኪ ጠፍዓ፡፡
አምጣነ ቅኔ አልዓዛር እምነ መቃብር ተንሥአ፡፡
ፍቺ፡- ተአምር ሠሪው ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጫካ ውስጥ በተሠራ ጊዜ የሥላሴ እህት     የሥላሴ ጎረቤት (የዓልአዛር እህት) ኀዘንሽ ጠፋ፣ ቅኔ ዓልአዛር ከመቃብር ተነሥቷልና፡፡
ምሥጢር፡- በመሞት ላይ የነበረው የግዕዝ ቋንቋ በክቡር ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁ የባህል  ጥናት         ተቋም አማካይነት በመነሣትና በማደግ ላይ ነው፡፡
ሥላሴ
ኢትደመም ወኢታንንክር፣
መምህረ ሐዲስ ሐዲስ በመዋዕሊከ ሰረገላ
ነቢይ ኤልያስ እንዘ ያንሶሱ ክልዔተ፡፡
ላዕለ ታቦር ወላዕለ ገሊላ አሀተ አሀተ፡፡
እስመ ያንሶስው ወትረ ላዕለ እንዶዳም ምዕተ፡፡
ሰረገላቲሃ ለግዮን ድኅረ ተከሥተ፡፡
ፍኖተ ዮፍታሔ ነዊህ ሰረገላተ፡፡
ዘያተሉ ሠለስተ ሠለስተ፡፡
ፍቺ፡- መምህር ሐዲስ ዓለማየሁ በዘመንህ በነበረውና ሁለት ጊዜ ብቻ በተመላለሰው የኤልያስ ሰረገላ አትደነቅ፡፡ በታቦርና በገሊላም ኤልያስ በሰረገላ የተመላለሰው አንዳንድ     ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በእንደዳም ኪዳነ ምሕረት መንደር መኪናዎች መቶ ጊዜ ይመላለሳሉና፡፡ ይህም የሆነው የዐባይ ወንዝ ሰረገላ ረጅሙን የዮፍታሔ ንጉሤ መንገድ ሦስት ሦስት በማስከተሉ ነው፡፡
ምሥጢር፡- የነቢዩ የኤልያስን ሰረገላ የሚበልጥ መኪና በዛሬው ዘመን በደብረ ኤልያስና     በሐዲስ ዓለማየሁ የትውልድ መንደር (በእንዳዳም) በየቀኑ 100 ጊዜ ይመላለሳል፡፡ ይኸውም የጠጠር መንገድ የተሠራው በሥራ አስኪያጅ ስማቸው ድጋፍ መሆኑን ቅኔው ያስረዳል፡፡ ሐዲስ ዓለማየሁና ዮፍታሔ የተጠቀሱት የደብረ ኤልያስ ተወላጆች     መሆናቸውን ለማመልከት ነው፡፡
መወድስ
በከየት ራኄል ምድረ ጮቄ፣ አርዘ ልዕልና መዊዕ ሶበ በጊዜሁ ተግህደ፡፡
ወተናዝዞ ዐበየት በዘኢኮነ ልሙደ፡፡
በግብፅ እስመ ኢኮንዋ ውሉዳ ውሉደ፡፡
አመ አመ ፈርዖን ቤተ ፈርዖን፣
ቤተ እስራኤል ዩቶር በምድረ ኔጌቭ ተአንገደ፡፡
ሙሴሂ ዲፕሎማሲ ኅበ ምድረ ግብፅ ወረደ፡፡
ሞገሰ ጎጃም ከነዓን ሶበ ተትሕተ ወተዋረደ፡፡
አምጣነ መለስ አሮን በመዋዕሊሁ ተፈቅደ፡፡
ይኩኖ አፈጉባኤ ወጸጋ ሔኖክ መዋግደ፡፡
ፍቺ፡- የከፍታ ዛፍ በጊዜው በተጋዘ በተወገደ ጊዜ የጮቄ ምድር ራኄል አለቀሰች፡፡ ልማዳዊ ባልሆነ ነገርም መናዘዝን እምቢ አለች፡፡ በግብፅ ልጆቿ ልጆች አልሆኑዋትምና፡፡ ዲፕሎማሲ ሙሴም ወደ ግብፅ የወረደው የጎጃም ሞገስ ከነዓን በመዋረዱ ነው። ከዚህም የተነሣ በዘመኑ አሮን መለስ አፈጉባኤና የጸጋ ቀንበር እንዲሆነው ተፈቀደ፡፡
ምሥጢር፡-
ውሃ በጮቄ ተራራ ላይ የነበረውን ዛፍ እየገነደሰ ወደ ምድረ ግብፅ እንደወሰደው ማለት ቀደም ሲል ጥቅጥቅ ደን የነበረው የጮቄ ተራራ በአሁኑ ሰዓት ዛፍ አልባ እንደሆነ ቅኔው ያሳያል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ዐባይን መገደብ ማስፈለጉና በዲፕሎማሲ ለመፍታት በተደረገው ጥረት አሮን የሙሴ አፍ ሆኖ እስራኤልን እንደረዳቸው ሁሉ፣ መለስም የዲፕሎማሲ አፍ፣ የሔኖክ ጸጋ ሆኖ በመሥራቱ ሁኔታዎች እንደተለዋወጡ ያሳያል፡፡ ሄኖክ የተጠቀሰው ፈጣሪ በጸፍጸፈ ሰማይ ላይ ምሥጢራትን በገለጠለት ጊዜ ሔኖክ ፈጣሪ የገለጠለትን ምሥጢር  ለመሸከም ስለአልቻለ “ኦ አኅዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ” ብሎ መጸለዩን ለማሳየት ነው፡፡ ያልተቻለው በመለስ እንደተቻለ ቅኔው ያሳያል፡፡ ሙሴ የተጠቀሰውም ወደ እስራኤል ፈጣሪ ሲልከው እኔ ኮልታፋ ነኝ ብሎ ሲናገር፣ አሮን ወንድምህ አንደበት ይሆንሃል ብሎ ነግሮት ነበር፡፡ መለስም የዲፕሎማሲ አፍና የአፍሪካና የዓለም አንደበት ሆኖ የሠራ መሆኑን በቅኔው ተመሥጥሯል፡፡
በአጠቃላይም አቶ ስማቸው “የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ” እንዲሉ፣ በአሁኑ ሰዓት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲን እንደ ዘራፊ በቅኔ፣ እንደ ቦርድ አባል በአስተዳደር፣ በምክርና በውሳኔ ሰጭነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡   

Published in ጥበብ

አቶ ገብረየሱስ ኢጋታ (የጊፍት ሪል እስቴት መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር)

ጊፍት ሪል እስቴት ባለፉት አስር ዓመታት በቤቶች ልማት ዘርፍ የነበረውን ተሳትፎ  እንዴት ይገልጹታል?
ጊፍት ሪል እስቴት በኢትዮጵያ ያለው ዕድገትና የልማት ፍላጎት የወለደው ኩባንያ ነው። በኢትዮጵያ በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ብዛትና ሃገሪቱ እያስመዘገበች ካለው የኢኮኖሚ እድገት ጋር በተያያዘ የዜጎች የመኖሪያ ቤት ጥያቄ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ምንም እንኳን ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ይህንን እያደገ የመጣ ፍላጎት ብቻውን ሊፈታው እንደማይችል ተገንዝቧል። ስለሆነም የግሉ ዘርፍ በቤቶች ልማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ መሬት በረጅም ጊዜ በሚከፈል ሊዝ ከማቅረብ ጀምሮ አንዳንድ ማበረታቻዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ጊፍት ሪል እስቴትም ሲኤምሲ እና አያት አካባቢ ከመንግስት በተረከበው 16.3 ሄክታር መሬት ላይ 261 የተለያየ አይነት ያላቸው ዘመናዊ ቪላዎችን፣ታውን ሃውሶችንና ሮው ሃውሶችን  እንዲሁም ሁለት መቶ ዩኒት ያላቸው 44 ብሎክ አፓርትመንቶችን ለመገንባት እቅድ ይዞ፣ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ያስተላለፈ ሲሆን አሁንም በመጠናቀቅ ላይ ያሉትን ጨምሮ አዳዲስ ግንባታዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።  ጊፍት እንደ ግሩፕ ኩባንያ በኮንስትራክሽን፣በቤቶች ልማት፣በንግድና በማምረቻ ኢንደስትሪ ዘርፍ ከሚያንቀሳቅሳቸው አራት ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ግዙፉ ኢንቨስትመንቱ ይኸው የሪል እስቴት ኩባንያው ሲሆን የሚያከናውነው ግንባታ አጠቃላይ ካፒታልም 2 ቢሊዮን ብር ይደርሳል። በግንባታው ሂደት እስከ 2 ሺህ የሚደርሱ ሰራተኞችን በማሳተፍም ከፍተኛ የስራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሃገር በቀል ኩባንያ ነው።  
በኢትዮጵያ ያለው የሪል እስቴት ዘርፍ እድገት አዝጋሚ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ከ5 ዓመት በፊት የተደረጉ አንዳንድ ጥናቶች፣ሪልእስቴት ከኮንስትራክሽን ሴክተር ጋር ተዳምሮ ከአጠቃላዩ የሃገር ውስጥ ምርት  14.9 በመቶ  ድርሻ እንደነበረውና ዘርፉ በአማካይ በየዓመቱ ከ10 በመቶ በላይ እድገት እንዳስመዘገበ ያሳያሉ። ሁለቱ ተደጋጋፊ ዘርፎች በነዚሁ ዓመታት ብቻ ሃገሪቱ ካስመዘገበችው ከ11 በመቶ በላይ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ 1.5 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይዘው ነበር። አሁን አዲስ ጥናት ቢደረግ ይህ አሃዝ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር አልጠራጠርም። ሪልእስቴቱ ከኮንስትራክሽን ኢንደስትሪው ጋር ተጣምሮ የሃገር ውስጥ ምርት (GDP) መጠንን ከፍ ማድረጉ አይካድም።
ሪል እስቴት በግልም ይሁን በመንግስት የሚካሄዱ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ልማትን የሚያካተት ዘርፍ እንደመሆኑ እኔ በበቂ ሁኔታ አውቀዋለሁ በምለው የግል ሪልእስቴት ዘርፍ ላይ ብቻ አትኩሬ ጥያቄውን ብመልስ ተገቢ ይሆናል። የዘርፉ ዕድገት አዝጋሚ ነው፣ አይደለም ወደሚል መደምደሚያ ለመድረስ ጥናት ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ነገር ግን ሪል እስቴት እንደ አንድ ኢንደስትሪ  በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የራሱ የሆነ ድርሻ ይዞ መንቀሳቀስ  ከጀመረበት ሁለት አስርተ ዓመታት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ምን ሰርቷል፣ ምን ያህል ኩባንያዎችንስ ማንቀሳቀስ ችሏል የሚለውን ካየን የምናገኛቸው አሃዞች ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ መሆኑን ይመሰክራሉ። ከ2003 ዓ.ም ወዲህ ባሉት አራት አመታት ብቻ 120 ኩባንያዎች በሪልእስቴት ኢንደስትሪ ውስጥ ለመሳተፍ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ማውጣታቸውን መረጃዎች  ይጠቁማሉ። ከነዚህ ፍቃድ የወሰዱ ተቋማት ውስጥ ጥቂቶቹ ወደ ሥራ ገብተዋል። እንግዲህ አንጋፋ ከሆኑት ጊፍት ሪል እስቴትን ከመሳሰሉ ኩባንያዎች ጋር ሲደመር በተለይም ከሚያንቀሳቅሰው በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ካፒታል ጋር ሲነጸጸር ይህ በግሉ ዘርፍ የሚካሄድ ግዙፍ ኢንቨሰትመንት  በኢኮኖሚው እድገት ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል።
ያም ሆኖ የዜጎችን የቤት ፍላጎት ከማሟላት አንጻር ምን ያህን ተንቀሳቅሰናል የሚለውን ካየን፣ የግሉም ይሁን የመንግስት ሪልእስቴት ዘርፍ “የላቀ” የሚባል ደረጃ ላይ አልደረሰም። ይህም ሃገራዊ ፍላጎቱ ካለው አቅርቦት በላይ በመሆኑ  የተፈጠረ ክፍተት ነው። የግል ሪል እስቴት ዘርፍ እድገት የህዝቡን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ከማሟላት አንጻር ከታየ በርግጥ ገና ብዙ ይቀረዋል። በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ አሁንም አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ይህም ገበያው ሰፊ እንዲሆን አድርጎታል። አሁን ያለው የሪል እስቴት ዘርፍ በብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ይህንን ገበያ ለመሸፈን በሚያስችል አቅም ላይ እንዳልሆነ ነው የምገነዘበው። ነገር ግን ዘርፉ የበለጠ ድጋፍ ከተደረገለት የሚገነባቸውን ቤቶች ዓይነትና ደረጃ በማስፋት በከፍተኛ ብቻ ሳይሆን በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ዜጎች የቤት ፍላጎት በየደረጃው  ለሟሟላት የሚያስችል አቅም አለው።
  በእርስዎ አተያይ ለሪል እስቴቱ  እድገት ጎታች  ናቸው የሚሏቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፣ሪልእስቴቱ እንደማንኛውም የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ዘርፍ እድገቱን የሚገቱ ውጫዊና ውስጣዊ እንቅፋቶች አሉበት። ከውጫዊ ችግሮቹ ብንነሳ በአሁኑ ወቅት ያለው የመሬት አቅርቦት ማነስና የዋጋ መናር ስራውን አዋጪ ስለማያደርገው አዳዲስ ተዋናዮች በቤት ልማት ኢንደስትሪው ውስጥ እንዳይገቡ፣ነባሮቹም ስራቸውን እንዳያስፋፉ ምክንያት ይሆናል። ከመሬት አቅርቦት ማነስ ጋር በተያያዘ ብዙ አልሚዎች በተለይ ከተማ ውስጥ ለሚያካሂዷቸው የመኖሪያና ንግድ ቤት ግንባታዎች የሚሆን መሬት ከግለሰቦች ላይ በውድ ዋጋ ቦታ ለመግዛት ተገድደዋል። ይህም የቤት መሸጫ ዋጋቸው ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። በሌላ በኩል የኮንስትራክሽን ማቴሪያል አቅርቦት ማነስና ዋጋውም በየጊዜው ማሻቀብ በሪል እስቴት አልሚዎች ላይ የተጋረጠ ዋነኛው ችግር ነው። አልሚዎች ከደንበኞቻችን ጋር  በገባነው ውል መሰረት ግንባታውን በተባለው ጊዜ አጠናቀን እንዳናስረክብ በየጊዜው የሚከሰቱት የግንባታ እቃዎች እጥረት ጎታች ምክንያት እየሆነብን ነው። ይህ እጥረት የፈጠረው የዋጋ ልዩነት ደግሞ በግንባታ ዋጋው ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ስለሚያስከትል የአልሚዎችን አትራፊነት ከመቀነሱ ባሻገር በኮንትራት ጊዜው ውስጥ የሚፈጠረው የዋጋ ጭማሪ (price escalation) ደንበኞች አስቀድመው ከተዋዋሉበት  የቤት ግዢ ዋጋ በላይ እንዲከፍሉ ያስገድዳቸዋል። ይህም ሁለቱንም ወገን ተጎጂ ያደርጋቸዋል።
በሶስተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው የዘርፉ ዕድገት እንቅፋት የፋይናንስ አጥረት ነው።  ሪል እስቴት ግዙፍ ኢንቨስትመንት በመሆኑ ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ይጠይቃል። ኩባንያዎች ከደንበኞች ከሚሰበስቡት የቅድሚያ ክፍያ ውጪ ሌላ የፋይናንስ ምንጭ የላቸውም። በሃገራችን እንደሌላው ዓለም ሞርጌጅ ባንኮች  ባለመኖራቸው ለሪልእስቴት ብድር የሚሰጥ ባንክ የለም። በዚህ ሳቢያ ዘርፉ ተለዋዋጩን የገበያ ዋጋ ለመቅደምና ጊዜውን ለመጠቀም የሚያስችለው የፋይናንስ አቅም የለውም። ከዚህ በተጨማሪም ሪልእስቴቶች ለግንባታ መሬት በሚረከቡበት የከተማ ማስፋፊያ አካባቢዎች እንደ መንገድ፣መብራት እና ውሃ ያሉ መሰረተልማቶች በጊዜ ባለመሟላታቸው በግንባታ ስራው ላይ ብቻ ሳይሆን በሚገነቡት ቤቶች ዋጋ ላይ ጭምር ከባድ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል። እነዚህ እንግዲህ ውጫዊ ከሆኑት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው።
ውስጣዊ ምክንያቶችን ስንመለከት ደግሞ የልምድ እጥረት መኖር፣የስራ ባህልና የስራ ላይ ስነምግባር አለመዳበር፣የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እጥረትና በዘርፉ ብቃት ያለውና የሰለጠነ ባለሙያ በገበያው ውስጥ እንደተፈለገው አለመገኘት ተጠቃሽ ምክንያቶች  ተደርገው መወሰድ ይችላሉ።
  አብዛኞቹ የሪል እስቴት ደንበኞች በውለታቸው መሰረት ቤታቸው በጊዜ ተጠናቆ መረከብ አለመቻላቸውን በተመለከተ ተደጋጋሚ ቅሬታ ያነሳሉ። ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ?
ከላይ ለመዘርዘር የሞከርኳቸው ውጫዊና ውስጣዊ  ችግሮች ለዘርፉ እድገት ማነቆ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ለደንበኞች ቅሬታ መነሳትም ምክንያት ሆነዋል። በርግጥ እያንዳንዱን ኩባንያ ወክዬ  ከደንበኞቻቸው ለቀረቡት ቅሬታዎች መልሱ ይህ ነው ማለት አልችልም። ግን የጋራ የሆኑና በኢንደስትሪው ላይ ተደጋግመው የሚታዩ ችግሮች ለደንበኞች ቅሬታ መከሰት ገዢ ምክንያት ሆነው ሲወጡ ይስተዋላል። ያም ቢሆን ግን በግሌ ውስጣዊም ይሁን ውጫዊ ምክንያት ማቅረብ የደንበኞችን ቅሬታ ለመሸፋፈን  እንደ ምክንያት  (Excuse factor) ሊቀርብ አይገባም ባይ ነኝ።
ደንበኛ ሁልጊዜም ትክክል ነው በሚለው መርህ አምናለሁ። ደንበኛው ከኩባንያው ጋር ውል ከገባና ተገቢውን ክፍያ ከፈጸመ በኋላ የሚፈልገው በየትኛውም መንገድ ይሁን በውሉ መሰረት ቤቱን መረከብ ነው። ነገር ግን ሪል እስቴት አልሚዎች ለደንበኞቻቸው የሚገነቧቸውን ቤቶች ዋጋ አውጥተውና ከዚያም ላይ ትርፋቸውን አስልተው ስራ ሲጀምሩ እጥረት የሚከሰትበትና በየጊዜው የሚያሻቅበው የኮንስትራክሽን ግብዓት ዋጋ እጃቸውን የሚያስርበት ሁኔታ አለ፡፡ ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ እንዳይንቀሳቀሱ ምክንያት ይሆናል። ያ ብቻ ሳይሆን የግብዓት ዋጋው እየጨመረ ሲመጣ የግንባታ ዋጋም የዚያኑ ያህል ከፍ ስለሚል  ዞሮ ዞሮ ውሉ በኮንትራት ጊዜ ውስጥ ለሚፈጠረው የግብዓቶች ዋጋ ንረት ደንበኛው ልዩነቱን እንዲከፍል ያስገድደዋል። ይህን ጊዜ ጫናው በሁለቱም ላይ ይወድቃል። የተገልጋይ እርካታም ይጠፋል። በዚህ ሳቢያ ግንባታዎች ለሁለትና ሶስት ዓመታት ሊጓተቱ ይችላሉ። ይህ የቢዝነሱን ባህሪ ኢ-ተዓማኒ የማድረግ አደጋ ስለሚጋርጥ ለኩባንያዎቹ ከባድ ፈተና ነው። እዚህ ላይ ደንበኞች ለችግሩ አስተዋጽዖ ስለሌላቸው የሚወቀሱበት ምክንያት የለም። ጫናው ሃገር አቀፍና የሁሉም ሪልእስቴት አልሚ ችግር ስለሆነ ልዩ ልዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመቀየስ  የደንበኛውን ፍላጎት ለማሳካት መስራት ግድ ይሆናል።
   በሌላ በኩል ዘርፉ ከዋጋው አንጻር ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ዒላማ ያደረገ በመሆኑ የብዙሃኑን የቤት ፍላጎት ከማሟላት አንጻር ያበረከተው አስተዋጽዖ አናሳ ነው የሚል ትችትም ይቀርብበታል። ይህን እርስዎ እንዴት ያዩታል?
ይህ ጥያቄ ታሳቢ ማድረግ  ያለበትን ዋና ነገር የዘነጋ ይመስለኛል። የመኖሪያ ቤት  (መጠለያ) በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ ያለ ዜጋ እንዲሟላለት ከሚፈልጋቸው መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ነው። መጠለያ የማግኘት ጉዳይ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን መብትም ጭምር ነው። በእርግጥ ፍላጎት በአቅም ላይ  የተወሰነ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ከተስማማን መንግስት በስፋት የሚያካሂደው የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች ግንባታ ታሳቢ ያደረገው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ነው። መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ደግሞ በአብዛኛው በማህበር በመደራጀት ወይም በተናጥል መሬት በመግዛት መኖሪያ ቤታቸውን ራሳቸው ይገነባሉ። በሌላ በኩል አቅም ያላቸውና ገንዘብ አውጥተው የተገነቡ ቤቶችን ለመግዛት የሚችሉ ዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት ደግሞ ብዙዎቹ የሪልእስቴት ኩባንያዎች በንጽጽር ከፍ ያለ ዋጋ የሚያወጡ መኖሪያ ቤቶችን ይገነባሉ። በዚህ መሰረት የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በየደረጃው ለማሟላት የሚሰሩ  አንቀሳቃሾች (Actors) ድምር ስራ በሃገሪቱ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ማቃለል ያስችላል ማለት ነው። ጉዳዩን በዚህ መልክ መረዳት ይቻላል።
  የውጭ ሪልእስቴት ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባት ለሃገር ውስጥ አልሚዎች ስጋት ነው ብለው ያምናሉ?
በቅርቡ ወደ ገበያው የተቀላቀሉትንና ለመግባት ፍላጎታቸውን ያሳዩትን የውጭ ሃገር ሪልእስቴት አልሚዎች ‘ስጋት’ ከማለት ይልቅ ‘ከባድ ተወዳዳሪ’ በሚል ብገልጻቸው ይስማማኛል። ይህንን የምለው ሁላችንም ማለት በሚያስችል መልኩ የሃገር ውስጥ ሪልእስቴት አልሚዎች ያለብንን የጋራ ችግር መሰረት አድርጌ ነው።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ገና በጨቅላ እድሜ ላይ ያለና ከልምድም ይሁን ከሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲሁም ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንጻር ብዙ የሚቀረው ዘርፍ ነው። በተለይ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ያለን ልምድ ብዙ የሚያግደረድር አይደለም። እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በሃገራቸው ባንኮች ፋይናንስ ስለሚደረጉ የገንዘብ እጥረት የለባቸውም። እንደ ሃገር ውስጥ ኩባንያዎች፣ ከደንበኞች በሰበሰቡት ገንዘብ ሳይሆን በራሳቸው አቅም ቤቱን ገንብተው በቀጥታ ወደ ሽያጭ ነው የሚሄዱት። ወዲያው ከፍሎ ወዲያው ቤቱን ለመረከብ ለሚፈልግ ሰው አማራጭ ይዘው መጥተዋል ማለት ነው። የግንባታ ጊዜያቸው ባጠረ ቁጥር የኮንስትራክሽን ግብዓት ዋጋ መናር ሊያስከትልባቸው የሚችለውን ግሽበት ያመልጡታል ማለት ነው። ስለዚህ አትራፊ ይሆናሉ። በሁለተኛ ደረጃ በዘርፉ የካበተ ልምድ ስላላቸውና ለግንባታ ቁልፍ የሆነውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ይዘው ስለሚመጡ እኛን የሚገጥመን አይነት ችግር አይገጥማቸውም። ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ በግንባታው ዘርፍ ወቅታዊ ነው የሚባለውን ቴክኖሎጂና ማሽን  ሁሉ መጠቀማቸው ነው። ይህም በአነስተኛ ወጪ፣በፈጣን ጊዜና በቀላል አሰራር ግንባታ እንዲያካሂዱ እድል ይፈጥርላቸዋል። በእነዚህ ብቃቶቻቸው ሳቢያ እንደ እኛ ባሉ በዘርፉ የተሰማሩ የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ላይ ከባድ ተወዳዳሪ ይሆናሉ ማለት ነው። የኩባንያዎቹን ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባት በመልካም አጋጣሚው ስናየው ደግሞ የቤት ፍላጎት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ገበያው ገና አልተነካምና ሜዳው ሁላችንንም ሊያጫውት የሚችል ነው። ሃገሪቱ ሰፊ ናት። ሪል እስቴቱ እስካሁን በአብዛኛው አዲስ አበባ ከተማ ላይ ተወስኖ የቆየ ነው። ስለዚህ የመጫወቻ ሜዳውን ወደ ክልል ከተሞችም ማስፋት ይገባናል። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ይዘው የመጡትን ቴክኖሎጂና እውቀት በጊዜ ሂደት ከኛ ጋር ለማዋሃድ እድሉ አለን። ሁላችንም እነሱ ወደደረሱበት ደረጃ ለመድረስ እየጣርን  የአቅማችንን በመስራትና ለደንበኞች የምንሰጠውን አማራጭ በማስፋት በዘርፉ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆነን ለመቀጠል የሚያስችሉን ብዙ እድሎች አሉ። በጊዜ ሂደት ዘርፉ እንዲያድግ ለማስቻል የነዚህ ኩባንያዎች መምጣት በጎ አስተዋጽዖ አለው ብዬ አምናለሁ። በርግጥ ቀላል ፉክክር እንደማይገጥመን ብረዳም ከወዲሁ ስትራተጂ ቀይሶ በገበያው ውስጥ ለመቀጠል ከተነሳን ግን  የተሻሉ አቅጣጫዎችን መቀየስ እንችላለን ብዬ አምናለሁ። የሪል እስቴቱ ዘርፍ ፈተናዎች ቢበዙበትም ሊጠቀምባቸው የሚገባ መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉትም መዘንጋት የለብንም።
በመጨረሻ ቀረ የሚሉት ሃሳብ ካለ ----
በዚህ አጋጣሚ መንግስት ለዘርፉ እስካሁን እያደረገ ላለው እገዛና እየገጠሙን ላሉት ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት ለሚያደርገው ጥረት ምስጋና  ማቅረብ እወዳለሁ። ይህ እንዳለ ሆኖ የሃገሪቱን የስራ አጥ ቁጥር በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ቀጣሪ በመሆን በኢኮኖሚው ውስጥ ጉልህ ሚና የሚጫወተውን የግል ግንባታ ዘርፍ አሁን ካለው በበለጠ መልኩ ትኩረት ሰጥቶ ሊደግፈው፣ በመልካም አስተደደርና በሌሎችም ዘርፎች የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታትም የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት ድጋፍና ክትትል ሊያደርግለት ይገባል የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እወዳለሁ።

Monday, 16 March 2015 09:44

የፀሐፍት ጥግ

አዲስ ሃሳብ እንደ ህፃን ነው፡፡ ከመውለዱ ይልቅ መፀነሱ ይቀላል፡፡
ቴድ ኮይሲስ
አንዴ በአዲስ ሃሳብ የሰፋ አዕምሮ ወደቀድሞ ቦታው ፈፅሞ አይመለስም፡፡
ኦሊቨር ዌንዴል ሆልሜስ
ሁሉም ስኬቶችና በልፋት የተገኙ ሃብቶች መነሻቸው ሃሳብ ነው፡፡
ናፖሊዮን ሂል
ሁሉም ነገር የሚጀምረው ከሃሳብ ነው፡፡
ኧርል ናይቲንጌል
ሃሳብ ማግኘት ስፒል ላይ እንደመቀመጥ መሆን አለበት፡፡ አዘልሎ የሆነ ነገር ሊያሰራህ ይገባል፡፡
ኢ.ኤል ሲምፕሶን
ሁሉም ታላላቅ ሃሳቦች አወዛጋቢ ናቸው፤ ወይም የሆነ ጊዜ ላይ አወዛጋቢ ነበሩ፡፡
ጊልበርት ሴልዴስ
ሃሳቦች በእርግጥም በዓለም ላይ እጅግ አደገኛ መሣሪያዎች ናቸው፡፡
ዊልያም አርቪሌ ዳግላስ
ብዙ ሃሳቦች ከበቀሉበት አዕምሮ ይልቅ ወደ ሌላ አዕምሮ ሲዛወሩ የተሻለ ያድጋሉ፡፡
ኦሊቨር ዌንዴል ሆልሜስ
ሃሳብ ሳይለወጥ ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ  አይተላለፍም፡፡
ሚጉልዲ ኡናሙኖ ይጁጉ
ሃሳቦች አሻፈረን ሲሉ ሰዎች ቃላትን ይፈጥራሉ፡፡
ማርቲን ኤች ፊሸር
ሁሉም ነገር ተብሏል፡፡ ግን ሁሉም ሰው አላለውም፡፡
ስታኒስሎው ሌስ

Published in ጥበብ