ግለ ታሪክም ሆነ የሕይወት ታሪክ ጽሑፎች ንጥጥር መቼም ቢሆን በጦር ጀግኖች ላይ ይበልጥ ማመዘኑን የምናጤንበት አንዱ አጋጣሚ ዘመናዊው የሕይወት ታሪክ አፃፃፍ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ማበቡ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዚያ ቀደም የነበሩትን ተረታዊና አንዳች መለኮታዊ ተቀብዖ ማጐናፀፍን አስወግደው፣ በሰው ውስጥ ያሉትን ጀግንነትና ፍርሃት፣ ሀዘንና ደስታ… ወዘተ ፍንትው አድርገው እንዲያሣዩ ግድ ብሎዋቸዋል፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያም በዘመነ ኢሕአዴግ ይህ የሥነ ጽሑፍ ዘውግ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ በየጊዜው እያበበ መምጣቱን እያስተዋልን ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራት ማህበረ ፖለቲካዊ መልክ በመቀየሩና የቀድሞው ሠራዊት ሽንፈት የአመራር እንጂ የጀግንነትና የሃይል እጥረት እንዳልሆነ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የታሰበ ሊሆን ይችላል ብሎ መላምቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
አብዛኞቹ የህይወት ታሪኮች የቀድሞውን መንግስት ሰራዊትና የኢህአዴግ ታጋዮችን የሚያስቃኙ ሲሆን ሰሞኑን በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የተመረቀው የህይወት ታሪክ ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ መንግስት ያገለገሉትን የሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ ሕይወትን የሚያሳይ ነው፡፡
በሁለት መቶ ሰማንያ ስድስት ገፆች የተጠረዘውና በሺበሺ ለማ የተፃፈው ይህ የሕይወት ታሪክ “ቆፍጣና ወታደር ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ” የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል፡፡ የመጽሐፉ ሽፋን ቡናማና ነጭ ቀለም የተጐናፀፈው የጄኔራሉ ፎቶግራፍ ሲሆን ከውጭ ሲታይ አንዳች ስሜት ይፈጥራል፡፡ በተለይ ታሪኩን አንብበው ደግመው ፎቶግራፉን ሲመለከቱት፤ የጄኔራሉ አስተያየትና ቅጭም ያለ ፊት የሚነግረን ወሬ፣ የሚያሣየን ሥዕል አለ፡፡ ሕሊናችን ውስጥ አንዳች ነገር ይደውላል፡፡ ሰውየውን ፎቶግራፉ ይተርካቸዋል፡፡
ጄኔራሉ በ1910 ዓ.ም ወደዚህ ምድር ከመጡ ጀምሮ፣ ያለፉበት የሕይወት ጐዳና ብዙ ነገር ያስተምረናል፡፡ አንድ የሕይወት ታሪክ የአንድን ሰው ታሪክ ዱካ እየተከተለ በተረከ ቁጥር የሚነካቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ አውዶች መልክና ጠረን ማሣየቱ ተገቢ ስለሆነ የእኒህን ጀኔራል ሕይወትም ስንከተል በዘመኑ ማህበረ ፖለቲካዊ አውድ ውስጥ የነበሩ አስተሳሰቦች፣ ንቅናቄዎችና ፍልሚያዎችን ሁሉ እናያለን፡፡
በተለይ ደግሞ ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ በኮሪያና በኮንጐ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ የኢትዮጵያና ከዚያም በኮንጐ የአስራ ሰባቱ ሀገራት ሠራዊት አዛዥ በመሆን ስላገለገሉ የወቅቱን አለም አቀፋዊ ፖለቲካ ሣይቀር እንቃኝበታለን፡፡ በኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴና የነፃነት ጥያቄ ውስጥ ሁልጊዜ የሚነሳው የመንግስቱ ንዋይና አበሮቹ ትግል ታሪክም በመጽሐፉ ውስጥ ተካትቷል፡፡
በቀውጢው ቀናት በተለያየ ጐራ ቢቆሙም ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬና ብርጋዲዬር ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ከልጅነታቸው ጀምሮ አብረው ያሳለፉ፣ በአንድ የጦር ትምህርት ቤት የተማሩና ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ዘመንም አብረው የተሰደዱ ባልንጀራሞች ነበሩ፡፡ ጄኔራል ከበደና ጄኔራል መንግስቱ እጅግ የሚቀራረቡ እንደሆነ ለማየት ብርጋዲየር መንግስቱ ንዋይ፤ ሻለቃ ለነበረው ወጣት ጓደኛው የፃፈውን ደብዳቤ ማጤን በቂ ነው፡፡
“ለምወድህና ለፍቅሬ ሻለቃ ከቤ ገብርነት” ይላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ “አዲስ አበባ ስትመጣ ሙዝ ሳትይዝ እንዳትመጣ” የሚል መልዕክትም ይዟል - ደብዳቤው፡፡  
መጽሐፉ የመረጃ ችግር የለበትም፡፡ መረጃዎቹም የግልና የመስሪያ ቤት ደብዳቤዎችን የያዙ በመሆኑ ብዙ ጥርጣሬን አይፈጥሩም፡፡ በተለይ ደግሞ የእጅ ጽሑፎቹና ፊርማዎች ያሉባቸው ደብዳቤዎች የመረጃዎቹን ተዓማኒነት ያጎሉታል፡፡
የመጽሐፉ ባለታሪክ በኢትዮጵያ የጦር ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ተማሪ ሲሆኑ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ በሲቪል ሹመኝነት የባሌ አውራጃ ገዢ፣ የአሰብ ፌደራሉ መንግስት የወደቡ ሃላፊ፣ የኦጋዴን አውራጃ ገዢ ሆነውም ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ባለቤታቸው ደስታ ገብሩም፤ የከንቲባ ገብሩ ልጅ በመሆናቸውና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ስላላቸው በዚህም በኩል መጽሐፉ የሚያሣየን ሌላ ገጽታ አለ፡፡ በብዙዎች የሚታወቁት ከንቲባ ገብሩ በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ በኢየሩሳሌምና አውሮፓ ለአሥር ዓመታት ያህል ዘመናዊ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገር ከተመለሱ በኋላ የገጠሟቸውን ፈተናዎች መጽሐፉ በግርድፉ ያሣያል፡፡
በመጽሐፉ ምረቃ ዕለት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ባቀረቡት ዳሰሳ ላይ እንደገለፁት፤ ታሪኩ የነካካቸው ማህበረ ፖለቲካዊና አጠቃላይ አውዶች ለአንባቢ የአንድ ሰው ታሪክ ብቻ ሣይሆን በዘመኑ የነበረውን ዓለም አቀፍ የሕይወት መልክ ሁሉ ያሣያል፡፡
የሌተና ጀኔራል ከበደ ገብሬ ታሪክን እያነበብን ስንዘልቅ ለንጉሱ የነበረንን አመለካከት መቀየራችን አይቀርም፡፡ ሰውየው ለሥልጣናቸው ብቻ ሳይሆን ለአገራቸው ለውጥና ዕድገትም ሲታትሩ እንደነበር እንጠረጥራለን፡፡ እኒህ የጦር መኮንን ለዚህ ታላቅ ሹመትና ስኬት የበቁት ከመኳንንት ቤተሰብ የተወለዱ ሆነው አልነበረም፡፡ ከአንድ ደሀ ቤተሰብ ተወልደው፣ አክስታቸው ቤት ተቀምጠው የተማሩ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዓይነት ሕይወት የነበራቸው ሰው ናቸው። ይሁንና ከንጉሰ ነገስቱ ጋር በቅርበት ለመስራትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጦር አዛዥ ሆነው በኮንጐ በማገልገል ታላቅ አድናቆት ከማግኘት ያገዳቸው ነገር አልነበረም፡፡ መኮንኑ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት የትሩማንንም የአድናቆትና የምሥጋና ደብዳቤ ለመቀበል በቅተዋል፡፡  ስለ ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ ሳነብ ያስተዋልኩትና ያስደነቀኝ ነገር ጄኔራሉ ነገሮችን ቀድመው የማየት ችሎታቸውና ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርጓቸው ጥረቶች ጉዳይ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ መካሪያቸው ባይበዛና የጄኔራሉን ምክር ቢያደምጡ ኖሮ ታሪካቸው በዚያ አይነት ክብር የጐደለው መንገድ አይቋጭም ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ካቀረቡዋቸው ሃሳቦች ባሻገር ወደ አብዮቱ መዳረሻ አካባቢ፣ የኤርትራ ፌዴሬሽን ውል መፍረስ ያመጣቸውን ችግሮች ነቅሰው ከነመፍትሔው ያስቀመጡበት መንገድ፣ የሠራዊቱን ቁጥርና መሠላቸት፣ የኑሮ ውድነትና የሶማሊያ የጦርነት አዝማሚያን በዝርዝር አውጥተው ንጉሱ ሊወስዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች ማስቀመጣቸው ጄኔራሉ ትልቅ የመሪነት አቅም እንደ ነበራቸው የሚጠቁም ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በኤርትራ ለሚኖሩት ሲቪል ወገኖቻችን የነበራቸው መቆርቆር የሰውየውን ቅንነት የሚያሳይ ነው፡፡ ገፅ 190 ላይ የሠፈረው የእጅ ጽሑፋቸው እንዲህ ይላል፡-
“በነዚህ ዘመናት ውስጥ /አሥር የጦርነት ዓመታት ማለታቸው ነው/ ከወምበዴዎች ጋር በመዋጋት ከጦር ሠራዊትና ከፖሊሶች የሞቱትና የቆሰሉት እንደዚሁም ከታማኙ ኤርትራዊ ብሔራዊ ጦር የተጐዱት ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ነው፤ አሁንም እየጨመረ ነው፤ እንደዚሁም በመንግስትን ንብረት ላይ የደረሰው አደጋ ከፍተኛ ከመሆኑም ሌላ በታማኙ ሕዝብ ሕይዎትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት አሁንም አለመቆሙ የጉዳቱን ክብደትና ግምት ከፍተኛ አድርጐታል፡፡” እያሉ ችግሮቹን ካሣዩ በኋላ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የኤርትራ ሕዝብ ከወምበዴው ጋር አብሮ ለመሠለፍ የሚጠብቀው ጊዜ ብቻ ነው ብለው አስጠንቅቀዋል፡፡
ከደብዳቤው መግቢያ ላይም፤ “የኤርትራን ነገር የወታደር ሃይል ብቻውን መፍትሔ ይሆነዋል ብሎ መዳማቱን ከመቀጠል ይልቅ በፅኑ ታስቦበት ሌላ ሁነኛ መፍትሔ እንዲፈለግለት የበኩሌን የቅን ልቦና ምክር በመስጠት…” እያሉ ወደ ቀጣዮቹ ስጋቶች ዘልቀዋል፡፡
ደርግ በታሪክ ከፈጸማቸው ትላልቅ ስህተቶች አንዱ፣ የእኒህን ጀግናና የሌሎች መሰሎቻቸውን ህይወት በከንቱ መቅጠፉ ነው፡፡ እጅግ በጣም ታላላቅ ሰዎች፣ ትልልቅ አእምሮዎች በጥይት ተማግደዋል፡፡ ጀኔራል አማን አምዶ ሚካኤል፤ “ሀገር በአሥር አለቃና ሃምሳ አለቃ እንዴት ትመራለች?” ባሉ ጊዜ ቆም ብለው የማሰብ አቅሙ ቢኖራቸው ኖሮ ይህ ሁሉ ቀውስ ባልመጣ ነበር፡፡
የፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን የሕይወት ታሪክ ካነበብኩ በኋላ የተሠማኝ የሀዘንና የቁጭት መንፈስ መቼም ከውስጤ አይወጣም፤ ይባስ ብለው ደግሞ እኒህን ሰው ሲጨምሩልኝ መንግስቱ ኃይለማርያም የሚመሩት መንግስት ምን ዓይነት ዕብደት ውስጥ እንደነበር ለመገመት አዳግቶኛል፡፡ ሺበሺ ለማ በፃፈው በዚህ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ መንግስቱ ኃይለማርያም የፃፉት አሰቃቂ ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡-
1ኛ/ ሌ/ጄኔራል አማን አምዶ ሚካኤል በዛሬው እለት ከመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ቤተ መንግስት በማምጣት ከእስረኞች እንዲቀላቀሉ፤
2ኛ/ በዋናው ከርቸሌ ለ54 ሰው በዶዘር ጉድጓድ እንዲቆፈር ሆኖ ከተራ ቁጥር አንድ እስከ 54 ያሉት ከፍተኛ የሲቪልና የጦር ባለስልጣናት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ከእስረኞች ተለይተው ለብቻ እንዲቆዩ፤
3ኛ/ ከሌሊቱ 8፡00/0200/ ሰዓት በወታደራዊ መኪናዎች ወደ ዋናው ከርቸሌ ተወስደው በአንድ ላይ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ እናስታውቃለን፡፡
በዚህ ደብዳቤ ላይ መንግስቱ ኃይለማርያም ስማቸውንና ፊርማቸውን አድርገው፣ማህተም መትተውበታል፡፡ ይህ ለሀገሪቱ የአሠቃቂ ዘመን መጀመሪያ ነበር፡፡ ያሳዝናል፡፡
በአጠቃላይ ሳየው “ቆፍጣናው ወታደር ሌተና ጀኔራል ከበደ ገብሬ” የሕይወት ታሪክ በመጽሐፍ ታትሞ መቅረቡ ለትውልድና ለሀገር የሚኖረው ፋይዳ ቀላል አይደለም፡፡ ከጀኔራሉ ታሪክ ብዙ ነገሮችን እንማራለን። ካለፉት መንግስታት ጥንካሬና ድክመት የምንማረው ቁም ነገርም አይጠፋም የሚል እምነት አለኝ፡፡
ምናልባት በታሪኩ ውስጥ እንደ ድክመት የምቆጥረው የልጅነት ታሪካቸው በበቂ ሁኔታ ያለመካተቱ ነው፡፡ ካትሪን አንቶኒ ስለ የሕይወት ታሪክ አፃፃፍ ሲገልጹ፤ “It is one of the axioms of modern biography that no life is complete without its childhood” ብለዋል። ግድ ካልሆነ በቀር ባይዘለል ይመረጥ  ነበር፡፡ በተለይ የሕይወት መሠረት የሚጣልበት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትረካ ከሌለ ብዙ ሥነ ልቡናዊ ሥዕሎች ሊሠወሩብን ይችላሉ፡፡ ለስኬትም ሆነ ለውድቀት ይህ ዕድሜ ምሠሦ ነውና! ምናልባት ግን ታሪኩ የተፃፈበት ጊዜ ጀኔራሉ በሕይወት ከነበሩበት 40 ዓመታት ያህል ስለራቀ መረጃ ማግኘቱ ከባድ እንደሆነባቸው መጠርጠር ጥሩ ነው፡፡
ሌላው ምዕራፍ 1 ላይ ያለው የመግቢያው አንቀጽ የታሪኩ ጅማሬ አካል ሣይሆን መግቢያ መምሰሉ ለምን ልብ እንዳልተባለ አልገባኝም፡፡ “ታዳጊው ከበደ” ካለ በኋላ መቀጠል ያለበት ስለ ከበደ እንጂ ስለ የሕይወት ታሪክ አጻጻፍ ወይም ትረካ መሆን አልነበረበትም፡፡ እኔ ሁለቱ አንቀፆች መግባት አልነበረባቸውም ባይ ነኝ፡፡
በተረፈ የመረጃ ጥንቅሩ፣ የታሪኩ ቅደም ተከተልና ፍሰት ጥሩ ነው፡፡ ከሁሉ ይልቅ የኒህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ታሪክ ማወቄ ደስ አሠኝቶኛል፡፡ በውስጤ ከፍተኛ ሀዘንና ቁጭት ቢያሣድርብኝም የዚህ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሕይወትም መልክ እንባና ሳቅ ስለሆነ “አሜን” ብሎ ከመቀበል ውጭ አማራጭ የለም፡፡ ታሪካችን በጨካኞች እጅ እየወደቀ አፈር ድሜ መጋጡ ግን አሳዝኖኛል፡፡

Published in ጥበብ
Monday, 16 March 2015 09:42

ካፌይን እና መዘዞቹ

ካፌይን አዕምሮን ለማነቃቃት የሚረዳና በተለይ በቡና፣ በሻይና በተለያዩ የለስላሣ መጠጦች ውስጥ በስፋት የሚገኝ ኬሚካል ነው፡፡ ካፌይን ከእነዚህ መጠጦች በተጨማሪ በቸኮሌቶች፣ በብስኩቶችና በተለያዩ የህመም ማስታገሻና የራስ ምታት መድሃኒቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ኬሚካል ሱስ የማስያዝ ባህርይው ከፍተኛ ነው፡፡ የተጠቀሱት መጠጦችና ምግቦች እንዲሁም መድሃኒቶች ካፌይን የመያዝ አቅማቸው እንደየሁኔታው የተለያየ ሲሆን በቡና ውስጥ የሚገኘው የካፌይን መጠን ከፍ ያለ ነው፡፡ አንድ ስኒ ቡና ከ100-150 ሚሊ ግራም ካፌይን በውስጡ ይይዛል፡፡ አንድ ሰው በቀን በአማካይ 80 ሚሊ ግራም ካፌይን ይወስዳል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከመጠን ያለፈ ካፌይንን መጠቀም ለከፋ የጤና ችግር ይዳርጋል፡፡ በካፌይን ሳቢያ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል የካፌይን ስካር (ኢንቶክሲኬሽን)፣ ሱሰኝነት፣ የእንቅልፍ ማጣትና ጭንቀት ይጠቀሳሉ፡፡  
የካፌይን ስካር (ኢንቶክሲኬሽን)
ከ250 ሚሊ ግራም በላይ የሆነ ካፌይን ከተወሰደ የካፌይን ስካር ይጀምራል፡፡ የዚህ ችግር ምልክቶች ጭንቀት፣ መቅበጥበጥ፣ የህሊና መረበሽ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማላብ፣ የሽንት መብዛት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ እጅና እግርን የመውረር ስሜት መኖርና መነጫነጭ ናቸው፡፡ የካፌይን መጠኑ እየጨመረ ከሄደ እና 1000 ሚሊ ግራም ከደረሰ የአፍ መኮላተፍ፣ የሃሳብ መደነጋገርና የልብ ትርታ መዛባት ሊከተል ይችላል፡፡ መጠኑ ከዚህ እየጨመረ ከሄደም ድንገተኛ የልብ ምት መቆም (ሞትን) ሊያስከትል ይችላል፡፡
የካፌይን ሱሰኝነት
ራስ ምታት፣ ድብርት፣ ጭንቀት፣ ድካም፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ የማለት ስሜት--- በካፌይን ሱሰኝነት ምክንያት የሚከሰቱ የጤና ችግሮች ናቸው፡፡
ይህ ችግር ካፌይኑ ከቀረ ከ10-12 ሰዓታት ውስጥ የሚጀምር ሲሆን ከጥቂት ቀናት ተደጋጋሚ ስሜት በኋላ ሊጠፋ የሚችል ነው፡፡
የእንቅልፍ ማጣትና ጭንቀት
መረበሽ፣ መነጫነጭ፣ በአንድ ቦታ ተረጋግቶ አለመቀመጥ፣ መርበትበትና መጨነቅ በካፌይን ሰበብ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ካፌይን ለእንቅልፍ ማጣት ሰበብ ከመሆኑም በተጨማሪ  ለድብርት፣ ለጭንቀትና ለውጥረት ዋንኛ ምክንያትም ነው፡፡
የመፍትሔ እርምጃዎች
የሚወሰደውን የካፌይን መጠን በአንድ ጊዜ ለመቀነስ መሞከር አይመከርም፡፡ ይልቁንም ዕለት በዕለት ቀስ እያሉ የሚወስዱትን የካፌይን መጠን በመቀነስ በሂደትም ማቆም በካፌይን ሰበብ ከሚደርሱ የጤና ችግሮች ሊታደገን ይችላል። ካፌይን የሌለባቸውን ምግቦችና መጠጦች ለይቶ በማወቅ እነሱ ላይ ትኩረት በማድረግ መጠቀም፣ ራስን በሌሎች ነገሮች ለማዝናናት መሞከርና ውሃን አብዝቶ መጠጣት በካፌይን ሳቢያ የሚከሰቱትን የጤና ችግሮች ለማስወገድ ይረዳል፡፡

Published in ዋናው ጤና
Monday, 16 March 2015 09:40

የውሃ ህክምና ፈውስ

የውሃ ህክምና (ሃይድሮቴራፒ) ጥንታውያን ግሪኮች፣ ግብፆችና ሮማውያን ከበሽታ ለመፈወስ  ሲጠቀሙበት የኖሩት ህክምና ሲሆን በቀላሉ ሊገኝ የሚችልም ነው፡፡ ውሃ በፈሳሽ፣ በበበረዶና በጋዝ መልኩ የተለያዩ ጠቀሜታዎችን ይሰጣል፡፡ ቀዝቃዛ፣ ሙቅና ፍል ውሃም አገልግሎቱ ለየቅል ነው፡፡
ውሃን በመጠጣት የሚገኝ ፈውስ
 ንፁህ ውሃን በመጠጣት ለህመም ፈውስ ማግኘት ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ሲተገበር የቆየ ህክምና ነው። ውሃን መጠጣት የሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅምን                                                                                ያዳብራል፡፡ ውሃን በመጠጣት የኩላሊት፣ የጨጓራ፣ የፊኛ፣ የመገጣጠሚያ አካላት፣ አንጀትና ጣፊያ በሽታዎችን፣ ኪንታሮት፣ የሳንባ ምች፣ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችን፣ የጡንቻና አጥንት ጤና ችግሮችን ማስወገድ ይቻላል፡፡
ሁልጊዜ ጠዋት ቁርስ ከመመገባችን በፊት ከአምስት ብርጭቆ ያላነሰ ውሃ ብንጠጣ ለተለያዩ ውስጣዊ የጤና ችግሮቻችን መፍትሄ እናገኛለን፡፡ ውሃ በተፈጥሮው የአሲድነት ፀባይ የሌለው በመሆኑ ለሰውነታችን ውስጣዊ ኡደት መቀላጠፍ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በአግባቡ ሳይሰለቀጡ ወደ አንጀታችን የሚገቡ ምግቦች በቀላሉ እንዲብላሉና በጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ውሃ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡
ውሃን በመነከር የሚገኝ ፈውስ
በጣም የቀዘቀዘ ውሃ ማይግሪን ለተባለው ራስ ምታት ፍቱን መድኀኒት ነው፡፡ ህመሙ በሚነሳበት ወቅት በጣም የቀዘቀዘ ውሃን ለአምስት ደቂቃዎች ያህል አናት ላይ በመያዝ ህመሙን ማስታገስ ይቻላል፡፡
ቀዝቃዛ ውሃ ለአለርጂ፣ ለጡንቻ መዛል፣ ለአዕምሮ መረበሽ (ለድብርት)፣ ለውጥረት፣ ለትኩሳትና ለሌሎችም በሽታዎች ፍቱን መድኀኒት ነው፡፡ ውሃ በሞቃትና በፍል መልኩ ጥቅም ላይ ሲውል ደግሞ ለመገጣጠሚያ ችግሮች፣ ለጉንፋን፣ ለብርድ፣ ለኢንፍሉዌንዛ ፍቱን መድኀኒት ነው። የሙቀት መጠኑ 750c የሆነ ውሃ ህመም በሚሰማን ቦታ ላይ ማፍሰስ (መነከር) ከህመም እፎይታን ሊያስገኝ ይችላል፡፡
ውሃን በበረዶ መልክ መጠቀም  
በመገጣጠሚያ አካላት ላይ በአደጋ (መውደቅ፣ መጋጨት) ለሚደርስ ጉዳትና በዚህ ሳቢያ በሰውነታችን ላይ ለሚከሰት እብጠት፣ የጡንቻ መሸማቀቅ ወይም ውልቃት በረዶ ፈጣን ፈውስን ያስገኛል፡፡ በረዶ በተጎዳው ሰውነታችን ላይ ሲደረግ ከህመም እፎይታን ከማግኘታችንም በሻገር እብጠቱን ለመቀነስ ያስችላል፡፡
ውሃን በመታጠን መፈወስ
ውሃን አፍልቶ መታጠን (በጋዝ መልኩ) ለጉንፋን፣ ለሳል፣ ለኢንፍሉዌንዛና ለጉሮሮ ህመሞች ፈጣን ፈውስ ይሰጣል፡፡  
የውሃ ህክምና ጥንቃቄዎች
በውሃ ህክምና በመታገዝ ፈውስ ለማግኘት በምንሞክር ወቅት ያሉብንን የጤና ችግሮች በሚያባብስ መልኩ እንዳይሆንብን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ቁስለት ባለባቸው የሰውነት አካላት ላይ ሙቅም ሆነ ቀዝቃዛ ውሃ መጠቀም የለብንም፡፡
እርጉዝ ሴቶች በውሃ ህክምና ከመጠቀማቸው በፊት ከሃኪማቸው ጋር መማከር ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ ህክምናውን በብልት (በማህፀን አካባቢ) ላሉ ችግሮች መጠቀም የሚፈልጉ እርጉዝ ሴቶች ህክምናውን ከመጀመራቸው በፊት ሃኪማቸውን ማማከር ይገባቸዋል፡፡

Published in ዋናው ጤና

ኢህአፓም “አሲምባ”ን ማስጎብኘት ይችላል----

  ልጅ ያሬድ የተባለው ታዋቂ ኮሜዲያን ሰሞኑን በዋሽንግተን ሆቴል (የአዲስ አበባው ነው!) ባቀረበው የኮሜዲ ምሽት ላይ የታደመችው የሥራ ባልደረባዬ ሰምታ ካጣጣመቻቸው ቀልዶች ውስጥ  ጥቂቶቹን ስለነገረችኝ እኔም ለናንተ ላጋራችሁ፡፡ (“sharing is caring” አሉ!)
ወደ ልጅ ያሬድ ቀልድ፡- አንድ የሆነ ሰፈር ነው አለ፡፡  ሌላው ጋ 3 ብር የሚሸጠውን አንድ እንጀራ 4 ብር ነው የሚሸጡት ---- ለምንድን ነው እዚህ ሰፈር  4 ብር የሚሸጠው ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ ምን ቢሉት ጥሩ ነው --- እኛ ሰፈር ውሃ ስለሌለች ሊጡን በሃይላንድ ውሃ ነው የምናቦካው፡፡ (የጨረሰች  ቀልድ!)  
ባለፈው ሳምንት ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ስለ ህወሃት 40ኛ ዓመት በዓል ሳወጋችሁ አንዳንድ ተቃዋሚዎች፤ ኢህአዴግ በዓሉን ለምርጫ ቅስቀሳነት እየተጠቀመበት ነው የሚል ክስ መሰንዘራቸውን ጠቅሼ ነበር (ነገርዬው ባይሆን ለወቀሳ እንጂ ለክስ እንኳን አይበቃም!) የሆኖ ሆኖ ---- ተቃዋሚዎች ለምን እንዲህ ያለ ወቀሳ ሰነዘሩ ብዬ ሳሰላስል ሁለት መላ ምቶች ብልጭ አሉልኝ፡፡ አንደኛው፤ ህወሃት ለምን ለበዓሉ አልጠራንም የሚል የአበሻ ቅያሜ ቢጤ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ አይፈረድባቸውም፡፡ ለምን መሰላችሁ ----- ሱዳኖችንና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲን በሰበብ አስባቡ እየጋበዙ ለአገር ቤት ተቃዋሚ ጀርባ መስጠት ያናድዳላ፡፡ (ቀላል ያጨሳል!)  
በነገራችሁ ላይ በእንዲህ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች (የህወሃት 40ኛ ዓመትን ማለቴ ነው!) ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀውን የፖለቲካ ኩርፍያ (የኩርፍያ ፖለቲካም ያስኬዳል!) ለመስበር መትጋት እኮ ብልህነት ነው፡፡ (አረ ብልጥነትም ጭምር!) ፖለቲከኞቻችን ሌላው ቢቀር … ለአዲሱ  ትውልድ የሚያስረክቡትን አገር ማሰብ አለባቸው፡፡ (ኩርፍያ የሞላት አገር ማን ይረከባል!)
እናላችሁ----በተለይ የመንግስትን ስልጣን የያዘው ኢህአዴግ ተነሳሽነቱን መውሰድ አለበት ባይ ነኝ፡፡    (ከተቃዋሚም ቢገኝ አንጠላም!) አያችሁ ቢገባን እኮ---ለሰላምና ለፍቅር መሸነፍ ከማሸነፍ እኩል ነው፡፡ (ኧረ ኩርፊያው ይሰበር!) አሁንስ እኔ ለእነሱ ደከመኝ… (ስፖንሰር ከተገኘ “ኩርፊያው ይሰበር” የሚል የ6 ወር አገራዊ ንቅናቄ ለመጀመር አስቤያለሁ!)
ሁለተኛውን መላ ምት እንኳ ሳምንትም ጠቀስ አድርጌዋለሁ (የአርቲስቶች ደደቢትን መጎብኘት ማለቴ ነው!) ዛሬ ግን ችግሩን ብቻ ሳይሆን መፍትሄውንም ይዤአለሁ፡፡ ባለፈው ጠቀስ እንዳደረግሁላችሁ ተቃዋሚዎች በዚህ ነገር ደስ የተሰኙ አይመስሉም፡፡ ለዚህ ነው ኢህአዴግ በዓሉን ለምርጫ ቅስቀሳ ተጠቀመበት የሚል ወቀሳ የመጣው፡፡ (ሁሉ ነገር በአስተማማኝ ግምት ላይ የተመሰረተ ነው!)
ለነገሩ እስቲ ራሳችሁን በተቃዋሚዎች ቦታ አድርጋችሁ አስቡት፡፡ (ለአፍታ የእነሱን ጭንቅላት ልዋስ!) እናላችሁ--ለምሳሌ አርቲስቶችን ደደቢት ድረስ ወስዶ ማስጎብኘት ለምን አስፈለገ? (ያውም በምርጫው 11ኛ ሰዓት ላይ!) ግን እኮ ጥያቄው መቅረብ የነበረበት ለራሱ ለህወሃት ነው! የጉብኝቱ ዓላማ እንደተባለው ታሪክን ለትውልድ ማስተላለፍ ነው? (እንዴት አሁን ትዝ አላቸው?) ወይስ በምስኪንነት ሆድ አባብቶ አሊያም በጀግንነት ቀልብ ማርኮ የአርቲስቶችን ድምፅ ለመግዛት ነው? እኒህ ሁሉ ጥያቄዎችና መላምቶች  የእኔ አይደሉም … እኔ ለእነሱ የመታሁት መላ እንጂ!! (ራሴን በተቃዋሚዎች ጫማ ውስጥ አስገብቼ ማለት ነው!)
እናም ማንም ተቃዋሚ የሆነ (ያውም ደግሞ ያኮረፈ!) ከላይ ከቀረቡት ውስጥ ልቡ ወደ ሁለተኛው ጥያቄና መላ ምት እንደሚያደላ ሳይታለም የተፈታ ነው!! እናም ለዚህ ይሆናል የህወሃትን 40ኛ ዓመት  ለምርጫ ቅስቀሳ ተጠቀሙበት የሚለው ክስ (ይቅርታ ወቀሳ!) የመጣው፡፡ አሁን ወደ መፍትሄው እንግባ፡፡ የእኔ ሃሳብ ምን መሰላችሁ? ተቃዋሚዎችም ልክ እንደ ህወሃት የየራሳቸውን “ደደቢት” ለአርቲስቶች እንዲያስጎበኙ ዕድል መስጠት! (ከከተማ ሳይወጡ ደደቢት!) ግን ምን መሰላችሁ? ምንም እንኳን ተቃዋሚዎች እንደ ህወሃት በረሃ ገብተው ባይዋጉም አልታገሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ ዕውቅና ማግኘት፣ ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ አዳራሽ ወይም ሆቴል መከራየት፣ በየክልሉ ካሉ ትናንሽ የወረዳ ንጉሶች ጋር መወዛገብ፣ ሰላማዊ ፈቃዱ ህገወጥ ነው ከሚል የጸጥታ ኃይል ጋር መጋፈጥ (ዱላና ድብደባን ያካትታል!) ------ እኒህ ሁሉ የትግሉ አካል ናቸው፡፡
 ሌሎችም የትግል ቦታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ---ተቃዋሚዎች ፓርቲያቸውን ለመመስረት ሃሳብ የጠነሰሱበት ሥፍራ፣ በኢህአዴግ ካድሬ ተዋከብን የሚሉበት ቦታ፣በየጊዜው እነሱ ወይም ጓዶቻቸው የታሰሩበት፣(ቃሊቲ፣ዝዋይ፣ማዕከላዊ--ወዘተ) እነዚህ ሁሉ የእነሱ የትግል ቦታዎች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጋሩት አንድ የድል ቦታም አላቸው -የህዝብ ማዕበልን የሚያስታውሳቸው፡፡ መስቀል አደባባይ!! (የ97 ምርጫን ልብ ይሏል!) አያችሁ----ተቃዋሚዎችም ለአርቲስቶች ሊያስጎበኙት የሚችሉት ከበቂ በላይ የትግል ቦታና ታሪክ  አሏቸው፡፡ (የየራሳቸው ደደቢት እንደማለት!) በነገራችሁ ላይ የትጥቅ ትግሉን ያሸነፈው ኢህአፓ ቢሆን ኖሮ---- አርቲስቶቹ የሚጎበኙት ደደቢትን ሳይሆን አሲምባን ይሆን ነበር፡፡
 እናላችሁ … ተቃዋሚዎች አርቲስቶችን ሰብስበው የየራሳቸውን “ደደቢት” ቢያስጎበኙ ኩርፊያውን ለማርገብ የሚያግዝ ይመስለኛል፡፡ (አርቲስቶች የህዝብ ሃብት ናቸው ብዬ እኮ ነው!) በነገራችሁ … ላይ የህዝብ ሃብት ያልሆነ ነገር እኮ ፈልጋችሁ አታገኙም! ለምሳሌ መሬት የህዝብ ሃብት ነው (ይቅርታ እና የመንግስት!)፣ ቲቪና ሬዲዮ ጣቢያም የህዝብ ሃብት ነው፡፡ የኢህአዴግ ኢዶውመንቶች ራሳቸው - የህዝብ ሃብት ናቸው፡፡ የሥልጣን ባለቤት ማነው? ህዝብ ነው!! የመንግስት ሹማምንት የማን አገልጋይ ናቸው? የህዝብ!! ግን እኮ አርቲስቶች ሃብታቸውን ሲጠየቁ----ሃብታችን ህዝብ ነው ይላሉ፡፡ (ከምራቸው እንዳይሆን!)

የአከርካሪ አጥንት መዛባት ለአዕምሮ፣ ለሣንባና ለልብ ህመም ሊያጋልጥ ይችላል
ህፃናትም በችግሩ ተጠቂ እየሆኑ ነው

የአከርካሪ አጥንት ከትክክለኛ ሥፍራው አፈንግጦ ወይንም ወደ ጐን ታጥፎ ከመደበኛው የአጥንት አሰላለፍ ከ10 ድግሪ በላይ ተዛብቶ ከቆየ የከፋ የጤና ችግርና የአካል ጉዳት ያስከትላል፡፡ ችግሩ ተባብሶ ከቀጠለ መደበኛ የሰውነት ተግባራትን ከማወክም በላይ በአዕምሮ ነርቮች እንዲሁም በልብና በሳንባ ላይ ጉዳት ማስከተል ይጀምራል፡፡
በሣንይንሳዊ አጠራሩ ስኮላዮሲስ (Scoliosis) የሚባለው ይኸው የአጥንት መዛባት ችግር በጨቅላ ህፃናቶችና በታዳጊዎች ላይ የሚከሰትና ህመም ሣይኖረው ቆይቶ በመካከለኛው ዕድሜ ላይ ለከፋ የጤና ችግርና ለአካል ጉዳት የሚዳርግ ነው፡፡ ችግሩ በአብዛኛው ከ10-14 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎችን የሚያጠቃ ሲሆን ሴት ህፃናት ከወንዶች የበለጠ የችግሩ ተጠቂ ናቸው፡፡
የአለም ጤና ድርጅት የ2012 ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ የአከርካሪ መዛባት ችግር በመላው ዓለም በስፋት የሚታይና በርካቶችን ለከፍተኛ የጤና ችግርና ለአካል ጉዳት የዳረገ ሲሆን ችግሩ ይኼ ነው የሚባል ምልክት የሌለው በመሆኑ አብዛኛዎቹ ተጠቂዎች ችግሩ እንዳለባቸው የሚያውቁት ተባብሶ የአካል ጉዳትና ሌሎች የጤና ችግሮችን ሲያስከትልባቸው ነው፡፡ መረጃው እንደሚያመለክተው፤ 85 በመቶ የሚሆነው የአከርካሪ መዛባት ችግር መነሻ ምን እንደሆነ በውል የማይታወቅ ሲሆን የሆርሞን እና ነርቭ ስርአቶች መዛባት፣ ስርዓት የለሽ አቀማመጥ፣ የተደጋገመና ከአቅም በላይ የሆነ ክብደትን አዘውትሮ መያዝ፣ የአጥንትና ጡንቻ ስርዓት ችግሮችና የቅርብ ቤተሰብ የችግሩ ተጠቂ መሆን እንደ ዋና መነሻነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡  
ዕድሜያቸው ከ10-14 ዓመት የሚሆን ታዳጊ ወጣቶች አዶለሰንት ስኮሊዮሲስ በተባለው የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግር በስፋት የሚጠቁ ሲሆን ከውልደት አንስቶ እስከ 3 ዓመት ድረስ ባለ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚከሰተው (ኢንፋንታይል ስኮሊዮሲስ)፣ እንዲሁም ከ3 ዓመት እስከ 10 ዓመት በሚሆን የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚከሰተው (ጁቬናይል ስኮሊዮሲስ) ህፃናትን በማጥቃት ከሚታወቁት የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በህፃንነትና በታዳጊነት ዕድሜ ዘመናቸው ለገጠማቸው የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግሮች በወቅቱ መፍትሔ ያላገኙ ሰዎች በአዋቂነት የዕድሜ ዘመናቸው አብሮአቸው ለሚዘልቅ ቋሚ የጀርባ ህመም መዳረጋቸው እሙን ነው፡፡
የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግር የሚጀምረው መዛነፉ ከ10 ድግሪ በላይ ሲሆን ነው፡፡ የአጥንት መዛነፉ ጉዳይ እየጨመረ ሲሄድ የችግሩ ስፋትም የሚጨምር ከመሆኑም ሌላ በህክምና ከችግሩ የመላቀቅ ዕድልም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ የአጥንት መዛነፉ እየጨመረ ስለሚቀጥል በችግሩ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና ችግሮችም እየባሱ ይሄዳሉ፡፡
የአከርካሪ አጥንት አቀማመጥ መዛባቱ ከ70 ድግሪ በላይ ከሆነ ችግሩ የጐድን አጥንቶች ሣንባን እንዲጫኑት ስለሚያደርጋቸው የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል፡፡ ይህ ሁኔታ ተባብሶ ከቀጠለ ለአዕምሮ ነርቮች ጉዳት ስለሚዳርግ የአዕምሮ ጤና ችግርን ያመጣል፡፡ መዛባቱ ከ100 ድግሪ በላይ ከሆነ ደግሞ በልብ ላይ የከፋ የጤና ችግር በማስከተል ታማሚውን እስከሞት ሊያደርሰው ይችላል፡፡ ኦሶቲዮፔኒያ የሚባለው የአጥንት ጥንካሬ ማጣት ችግርም የሚከሰተው ህክምና ያላገኘ የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡
የችግሩ ምልክቶችና መፍትሔዎች
የአከርካሪ አጥንት መዛባት ችግር በኤክስሬይ የህክምና ምርመራ ዘዴ ሊታወቅ የሚችል ሲሆን የመዛባቱ መጠን ሰውየውን ጉዳት ላይ የሚጥል መሆን አለመሆኑን ባለሙያው ካመነበትና የመዛባቱ መጠን ከ20-40 ድግሪ የሚደርስ ከሆነ የታካሚው የአከርካሪ አጥንት ወደ ቦታው እንዲመለስ የሚረዳ ብረት በታካሚው ጀርባ ላይ ይታሰራል፡፡ ይህም በሂደት የተዛባው የአጥንት ክፍል ወደ ቦታው እንዲመለስ ይረዳል፡፡ የመዛባቱ መጠን ከ50 ድግሪ በላይ ከሆነ ግን ችግሩን ማስተካከል የሚቻለው በቀዶ ህክምና ብቻ ነው፡፡   

Published in ዋናው ጤና

ርዕስ፡ ቴአትረ ቦለቲካ - አሉባልታና የአገራችን የፖለቲካ
        ገመና
ጸሐፊ፡         ልደቱ አያሌው
የታተመበት ዓ.ም.፡     2007
የገጽ ብዛት፡     287
የመጽሐፉ ዋጋ፡     ብር 100

አሉባልታና ሚዲያ
አቶ ልደቱ አያሌው በቅርቡ ያሳተሙትን ሦስተኛ መጽሐፋቸውን አነበብኩት፡፡ ከግል ልምዳቸው ምሳሌዎችን እያጣቀሱ ያቀረቡት ታሪክ ራሳቸውን ንጹህ አድርጎ ከማቅረብም በላይ ማሕበረሰባዊ ትንታኔ የሚሰጥ ሥራ ነው፡፡ መጽሐፉ  በአገራችን የፖለቲካ ስሪት ውስጥ አሉባልታ ምን ያክል ስር የሰደደ ችግር እንደሆነ በማሳየት የጸሐፊውን ፖለቲካዊ ብስለት ይጠቁማል፡፡
ቴአትረ ቦለቲካ በአገራችን ፖለቲካ (ወይም በመጽሐፉ ርዕስ ላይ ጸሐፊው በገጠር የንግግር ዘዬ እንዳስቀመጡት  “ቦለቲካ”) አሉባልታ ምን ያክል ወሳኝ ድርሻ እንዳለው በሰፊው ያብራራል፡፡ ለአሉባልታ መስፋፋትም ሆነ ዕውነትን አጣርቶ ለሕዝቡ ባለማቅረብ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ነው። የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ውስጥ በሚዲያ የሚሰራጭ አሉባልታ ለምን ተዓማኒነት እንደሚያገኝ ለመግለጽ “እኔም እንደዚያው ነበርኩ” በማለት የራሳቸውን ልምድ ምሳሌ በማድረግ ያስረዳሉ፡፡ “ትግሉን በተቀላቀልኩበት ወቅት በጋዜጦችና በአንዳንድ የውጭ ሬዲዮ ጣቢያዎች ኢህአዴግንም ሆነ በወቅቱ የሽግግር መንግሥቱ አባል የነበሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በተመለከተ የሚወራውን አሉባልታ በሙሉ እኔ ራሴ ያለምንም መጠራጠር እውነት አድርጌ የማይ ሰው ነበርኩ፡፡
“በእርግጥ ለአብዛኛው ሕዝብ በሚዲያ የሚሰራጭ መረጃ ሀሰት ሊሆን ይችላል ብሎ መጠርጠር ራሱ የማይቻል ነገር ነው፡፡ ይህ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው አመኔታ መገናኛ ብዙኃኑ የሙያ ስነ ምግባር ያልጠበቀ ተግባር ለመፈፀም ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይም በጋዜጣና በሬዲዮ ውሸት የማይነገር መስሎ የሚታየው ግንዛቤው ዝቅተኛ የሆነው የሕብረተሰብ ክፍል፣ የሚባለውን ሁሉ ወዲያው አምኖ በመቀበል፣ እኔን በየአካባቢው ለማማትና ለመሳደብም ሆነ በእኔ ላይ ለማዘንና ለመዛትም ብዙም ጊዜ አልወሰደበትም”፡፡ በጋዜጠኞች ኢ-ሥነምግባራዊ በሆነ አሠራር በርካቶች የአሉባልታ ሰለባ ሆነዋል፡፡” ከእነኚህ ግለሰቦች ውስጥ አንዱ እንደሆኑ  የሚያስረዱት አቶ ልደቱ፤በአሉባልታ ምክንያት በደል የደረሰባቸው እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የትግል አጋሮቻቸውም ጭምር መሆናቸውን በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም ከምርጫ 97 ጋር ተያይዞ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ የተከሰተውን ክፍፍልና የጸሐፊውን ተሳትፎ በስፋት የሚዳስሰው ቴአትረ ቦለቲካ፤ የጋዜጠኛውን መረጃን አጣርቶ ሃቁን የማቅረብ ችሎታ በተደጋጋሚ ይጠይቃል፡፡  በ1996 ዓ.ም. ክረምት ላይ “የአቶ ልደቱ ወንድም የድሬዳዋ ከንቲባ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሾሙ” የሚል ዜና በወቅቱ ሕትመት ላይ በነበረው ኢትኦጵ ጋዜጣ ላይ መውጣቱን ጸሐፊው እንደ አንድ ምሳሌ ያነሳሉ፡፡ የተሾሙት ግለሰብ ከአቶ ልደቱ ጋር አንድ ዓይነት የአባት ስም ከመያዛቸው በቀር የሚጋሩት ነገር የነበረ ባይሆንም ይህ ዜና በተለይም በውጭ አገራት ጸሐፊው ኢህአዴግ መሆናቸውን ማሳመኛ ተደርጎ እንደቀረበ ይናገራሉ፡፡ በመጽሐፉ የተጠቀሱ ይህን መሰል ሌሎች በርካታ ምሳሌዎች ጋዜጠኞቻችን የግል አቋማቸውን ወደ ጎን በመተው ለሙያ ስነ ምግባራቸው ብቻ ተገዢ ለመሆን አለመቻላቸውን ለማሳየት ጸሃፊው ተጠቅመውበታል፡፡
በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርብ አሉባልታ ምን ያህል ለረጅም ጊዜ ዕውነት ሆኖ እንደሚቆይ የምንረዳው ደግሞ አቶ ሲሳይ አያሌው (የድሬዳዋ ከንቲባ ሆነው ሲሾሙ የአቶ ልደቱ አያሌው ወንድም መሆናቸው የተወራባቸው)”በሙስና ተጠርጥረዋል ተብለው መታሰራቸው ሲወራ አንድ የግል ፕሬስ ጋዜጠኛ ስልክ ደውሎ ‘ስለ ወንድምዎ ስለ አቶ ሲሳይ አያሌው መታሰር ምን አስተያየት አለዎት?’ ብሎ እንደጠየቃቸው ሲገልጹልን ነው፡፡
ጋዜጠኛው ከሚያገለግለው ሕዝብ የሚለየው አንድ ነገር ቢኖር ጠያቂነቱ ነው፡፡ ሌላው የተጣራ ዕውነትን ማዳረስ፡፡ ጋዜጠኛው በጥቂቱ እንኳን እነዚህን ሆኖ ካልተገኘ ለሕዝቡ የሚያቀርበው ሥራ አስከፊ የሆነ ውጤት የሚያስከትል ሊሆንም ይችላል፡፡ ይህም በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል እና በሌሎች አገሮች የታሪክ አጋጣሚ የታየ ነገር ነው፡፡ ከምርጫ 97 በፊትና በኋላ በነበሩት ሁነቶች ሁሉ ጋዜጠኞቻችን “ለምን?” ከማለት ይልቅ ያልተጨበጠ መረጃ ይዞ በማራገብ ሥራ ተጠምደው እንደነበር መጽሐፉ ምሳሌዎችን እየጠቀሰ ያሳያል፡፡ በ1995 ዓ.ም፣ መጨረሻ አካባቢም የሆነው ይሄ ነው፤ በቴአትረ ቦለቲካ ውስጥ እንደተገለጸው፡፡ በዚህ ወቅት ኢህአፓ አንድ አገር አቀፍ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት እንዲቋቋም ጥረት እያደረገ ነበር፡፡ አቶ ልደቱ አባል የነበሩበት ፓርቲ ጥምረቱ ውስጥ እንዲካተት ምንም ዓይነት ግብዣ ሳይደረግለት “ከተቃዋሚዎች ጋር አብሮ ሊሠራ የማይፈልግ አፈንጋጭ ነው” እየተባለ ሲወራ በወቅቱ መጠየቅ የነበረበትን ወሳኝ ጥያቄ ለማንሳት የሞከረ አንድም ጋዜጠኛ አልነበረም፤ “ኢዴፓ የወያኔ ተለጣፊ ነው ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ ለምን አብሮን ሊሠራ አይፈልግም እያላችሁ ትከሱታላችሁ?” የሚል፡፡     
የጠያቂነትና መርማሪነት ያለመኖር አንድ ነገር ነው። የሚዲያው ክፍተት ግን ከዚህም እንደሚብስ ይገልጻሉ- ጸሃፊው፡፡ በመጽሐፉ ገጽ 146 ላይ የቀረበው የቅንጅት የቅድመ ውሕደት ስምምነት ለዚህ እንደ ማስረጃ ቀርቧል። በ1998 ዓ.ም. “የተፈረመው ሰነድ አራቱ ድርጅቶች በምን ሁኔታና ቅደም-ተከተል ውህደት ለመፍጠር እንደተስማሙ የሚያሳይ ቢሆንም በማግስቱ ለኅትመት የበቁት አንዳንድ ጋዜጦች ግን “አራቱ ፓርቲዎች ተዋሃዱ” የሚል የተሳሳተ ዜና ለሕዝቡ ዘገቡ”። በወቅቱ ወረቀት ላይ ሰፍሮ የነበረውን ግልፅ መረጃ አንብቦ ለሕዝቡ ማቅረብ ሲቻል፣ጋዜጠኞች ግን በግድ የለሽነት የተዛባ መረጃን ዘግበው ለሕዝቡ አቀረቡ ሲሉ ጸሃፊው ወቅሰዋል፡፡    
የአቶ ልደቱ መጽሐፍ ሚዛናዊነትን መሳትና የመረጃን ትክክለኛነት ማጣራት የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ብቻ ችግር እንዳልሆነም ይገልጻል፡፡ አቶ ኤልያስ ክፍሌ በ1998 ዓ.ም. ከፓርቲ አባልነታቸው የተሰረዙ ግለሰብ ናቸው፡፡ ስለዚህም “በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ለመስጠት የሚያስችል የኃላፊነት ድርሻ አልነበራቸውም። …ነገር ግን የቅንጅት አመራሮች በታሰሩበት ወቅት አቶ ኤልያስን፤ ‘የቅንጅቱ ከፍተኛ አመራር አባል’ እየተባሉ በቪኦኤ የአማርኛው ፕሮግራም ቃለ-መጠይቅ ከመስጠትም አልፈው ለቢቢሲ የሀርድ ቶክ-ፕሮግራም ጭምር የቅንጅቱ ልዩ አማካሪ ነኝ በማለት ራሳቸውን ሹመው ቃለ-መጠይቅ ሰጥተዋል” (ገጽ 175)፡፡ ቢቢሲ ለጉዳዩ ሩቅ ስለሆነ ለዚህ አሳፋሪ ስህተት ይቅርታ ቢደረግለትም አቶ ኤልያስን “የቅንጅቱ ከፍተኛ አመራር አባል” ብሎ ቃለ መጠይቅ የወሰደው ጋዜጠኛ ግን በአገሩ ጉዳይ ላይ በወቅቱ ከፍተኛ ተደማጭነት በነበረው ተቋም ውስጥ እያገለገለ ከተሳሳተ ምንጭ የተገኘ መረጃ ማቅረቡ የጋዜጠኛውን ስነምግባር ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ስህተት ነው፡፡----  
ቴአትረ ቦለቲካ  ይህን የመሳሰሉ የጋዜጠኛው የሥነምግባር ጉድለቶች ያላቸውን ክስተቶች በድፍረት  ያጋልጣል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚሠሩ ጋዜጠኞች ችግሮች የሚመነጩት ከሚሠሩበት ተቋም ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ግላዊ ባሕሪ እንደሆነ ይደመድማል። “…የጋዜጠኞቻችን ችግር የሚመነጨው በዋናነት ከሚሠሩበት ተቋም ፖሊሲ ሳይሆን ከራሳቸው ግላዊ ባህሪ መሆኑን እንድንገነዘብ አርጎናል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ዲሞክራሲያዊ ባህሪና ሙያዊ ስነ-ምግባር በውስጡ እስከሌለ ድረስ  የኢትዮጵያ ወይም የአሜሪካ መንግስት መገናኛ ብዙሃን ተቀጣሪ ሆኖ በመሥራቱ ብቻ ከችግር ሊፀዳ እንደማይችል ታዝበናል”
በመጨረሻም በመጽሐፉ ውስጥ ከተጠቀሱት አጋጣሚዎች ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የጥምር መንግሥት ለማቋቋም ለመንግሥት ጥያቄ ያቀረበበትን እንደ የመጨረሻ ምሳሌ ላንሳ፡፡ በወቅቱ ሕትመት ላይ የነበረው አባይ የተሰኘ ጋዜጣ “ቅንጅቱና ህብረቱ የጥምር መንግስት እንዲቋቋም ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጥያቄ አቀረቡ” የሚል ዜና ይዞ ወጣ፡፡ ይህንን ጉዳይ በዝርዝር ያስቀመጡት አቶ ልደቱ፤”በወቅቱ ቅንጅት ውስጥ ተወካይ የነበሩትን እነ ዶ/ር ኃይሉ አርአያን ለምን ቅንጅቱ የጥምር መንግሥት ጥያቄ ለአቶ መለስ እንዳቀረበ ጠየቅናቸው፡፡ … ስለ ጥምር መንግሥት ጥያቄ የተደረገ ውይይትም ሆነ የተወሰነ ውሳኔ እንደሌለና በጋዜጣ ስለወጣው ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገለጹልን፡፡ በማግሥቱ ፓርላማ ይገባ-አይገባ? በሚለው አጀንዳ ላይ ለመነጋገር የቅንጅቱ አመራሮች ስብሰባ በግሎባል ሆቴል ተጠርቶ ስለነበር በዚያ ስብሰባ ላይ እኔ ራሴ በአካል ተገኝቼ ቅንጅቱ የጥምር መንግሥት ጥያቄ ማቅረብ አለማቅረቡን ጠየቅሁ” ይላሉ፡፡
የቅንጅቱ ሊቀመንበር የነበሩት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውልም እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እስካሁን እንዳልወሰኑና ቅንጅቱ እነሱን ሳያማክር እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ሊወስን እንደማይችል መልስ ይሰጣሉ፡፡ ከስብሰባው በኋላ አቶ ልደቱ በውጭ አገር ከሚገኝ አንድ የሚዲያ ተቋም በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ ቅንጅት የጥምር መንግሥት ጥያቄ እንዳላቀረበ ይናገራሉ፡፡ ይህ በሆነ በሦስተኛው ቀን አዲስ ዜና በመባል ይታወቅ የነበረው የእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋዜጣ ላይ በወቅቱ አቶ ልደቱ የተናገሩት “ውሸት እንደሆነና ቅንጅቱ ጥያቄውን ተነጋግሮበትና አምኖበት ለመንግሥት እንዳቀረበው” አድርገው ቃለ መጠይቅ ይሰጣሉ፡፡  
ታዲያ ጸሐፊው ይህንን አጋጣሚ ተርከው ሲጨርሱ፤ “በወቅቱ እኔን በጭፍን ከመተቸት በስተቀር ስለዚህ ጉዳይ እውነቱን አጣርቶ ለሕዝብ ለማሳወቅ የሞከረ አንድም ጋዜጠኛ አልነበረም” ሲሉ ቁልፍ ጥያቄ በውስጠ ታዋቂነት ያነሳሉ፡- የጋዜጠኛው ጠያቂነት እስከ ምን ድረስ ነው?    
መካተት ያልነበረበት
አቶ ልደቱ በምርጫ 97 በነበረው የፖለቲካ መነቃቃት ሕዝቡ “ማንዴላ” ብሎ የሰየመኝ ከፍታ ላይ እንዳልነበርኩ ባውቅም ጥቂት ቆይቶ ያው ሕዝብ “ከሀዲ ነው” እንዳለኝም ያክል አይደለሁም ይላሉ፡፡ ራሳቸውን እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እና ጠንካራ ጎኖች ያሉት ፖለቲከኛ አድርገው ማቅረባቸው እሰየው የሚያስብል ቢሆንም ቴአትረ ቦለቲካ ጸሐፊው ራሳቸውን ከመጠን በላይ አጋንነው ያቀረቡበት ትርክት እንዲመስል የሚያስችሉ ምዕራፎችን ከማካተት አላመለጠም፡፡ ከገጽ 117 ጀምሮ በአስር ገፆች የተተረከው ወ/ሮ የሺ የተባሉ ሴት ስለ ጸሐፊው ያዩት ሕልም አንዱ ነው፡፡ በተለይም ወ/ሮ የሺ ስለ ፖለቲካ ምንም ግንዛቤ የሌላቸው፤ አቶ ልደቱንም ከዚያ ህልም በፊት የማያውቁ፤ በፆምና በጸሎት ይኖሩ የነበሩ “የእግዜር ሴት” መሆናቸውን ስናነብ፣ ጸሐፊው ራሳቸውን በምን መልክ እያቀረቡልን ነው? ብለን እንድንጠይቅ ያደርጉናል፡፡ በአጭሩ ለማስቀመጥ፤ የወ/ሮ የሺ ሕልም ጸሐፊው የሆነ ዓይነት በእግዜር የተመረጡ ፖለቲከኛ እንደሆኑ አድርጎ ለማቅረብ ጥረት የተደረገበት መስሎ ይታያል፡፡ የተክለ ሰብዕና ግንባታ መሠረቱን ሲጥልም እንታዘባለን፡፡
በተጨማሪም አቶ ልደቱ ከፓርቲያቸው አመራርነት ሲሰናበቱ በባልደረቦቻቸው ከተበረከተላቸው የፎቶ ስጦታ ላይ የተወሰዱ የስንብትና የመልካም ምኞት መግለጫ ጽሑፎች ምንም እንኳ እነኚያ ግለሰቦች ስለ እሳቸው የሚሰማቸው ዕውነተኛ ስሜት ቢሆንም ለአንባቢው ማቅረቡ ግን ሌላ የተክለ ሰብዕና ግንባታ ከመሆን የዘለለ ትርጓሜ ሊገኝለት አይችልም፡፡
ሌሎቹ የመጽሐፉ ክፍሎች ጸሐፊው በትክክል ምን ዓይነት ሰውና ምን ዓይነት ፖለቲከኛ እንደሆኑ በሚገባ ያሳያሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ራሳቸውን ለመግለጽ ምንም ዓይነት አርያማዊ ጣልቃ ገብነት ላያስፈልጋቸው ይችል ነበር፡፡ የሌሎች ፖለቲከኞች ምስክርነትም እንደዚያው፡፡ ስለዚህም እነኚህ ሁለት ነጥቦች በቴአትረ ቦለቲካ ባይካተቱ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡  
መልዕክተ ልደቱ - ለወጣቱ
የተቃዋሚው ጎራ አሁንም ድረስ በ”ያ ትውልድ” የመጠፋፋት መንፈስ የሚመራ፤ አምባገነን፤ ተፎካካሪን እንደ ጠላትና ደመኛ የሚያይ፤ ልዩነቶችን ወደ ጎን ትቶ በአገር ጉዳይ ላይ በጋራ ለመሥራት የማይፈልግ የተበታተነ ኃይል እንደሆነ በተጨባጭ ማስረጃዎች ያቀረበው ቴአትረ ቦለቲካ ፤በአገራችን ፖለቲካ የቀረንን ተስፋ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው፡፡ በእርግጥ አብዛኛው ሕዝብ በፖለቲካው ተስፋ ከቆረጠ መሰነባበቱ የሚታወቅ ነው፤በተለይም ወጣቱ፡፡ በአገሩ ጉዳይ እንደማያገባው ሁሉ ፖለቲካዊ ስሜቱ እንዲጠፋ ለተደረገው ወጣት ተስፋ የሚኖር ከሆነም ተቃዋሚዎችንም ሆነ ገዢውን ፓርቲ የሚተቹት አቶ ልደቱ በሰጡት ምክር ውስጥ ነው “… በአሁኑ ወቅት በገዢው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚው ጎራ ዙሪያ የተሰለፉ የፖለቲካ መሪዎች የተሻለ ስርዓት ለአገራችን ያመጣሉ ብላችሁ አትጠብቁ፡፡ በእነሱ ሙሉ በሙሉ ተስፋ በመቁረጥ የራሳችሁን ዘመንና አስተሳሰብ ወኪል የሆነ አዲስና ብቁ የፖለቲካ አመራር ከውስጣችሁ ለመፍጠር ታገሉ” (ገጽ 183)
በአጠቃላይ ስናየው የአቶ ልደቱ መጽሐፍ ተራ መስሎ የሚታየን የአሉባልታ ጉዳይ ምን ያክል ስር የሰደደ አገራዊ ሳንካ እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ መጽሐፉ ተዳፍኖ የነበረን መረጃ በድፍረት ለሕዝብ ለማቅረብ የተደረገ ሙከራ ከመሆንም በላይ የማሕበረሰባችን አስተሳሰብና የምንይዘው አቋም ምን ያክል ባልተጣራ መረጃ ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚችል እና  በዚህ ጉዳይ ላይ ሚዲያው የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በዝርዝር የሚዳስስ መጽሐፍ ነው፡፡ ቴአትረ ቦለቲካ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች እንዲሁም በሚዲያ የቀረበለትን መረጃ ሁሉ እንደ ዕውነት ቆጥሮ ውሳኔ ላይ የሚደርሰውን ሕዝብ ጭምር የቤት ሥራ የሚሰጥ መጽሐፍ በመሆኑ ሊነበብ ይገባዋል እላለሁ፡፡   

Published in ህብረተሰብ

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ ኮሌጅ በስዕል ትምህርት በ1980 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ በአሁን ሰዓት የራሱን ስቱዲዮ አቋቁሞ የተለያዩ የስዕል ሥራዎቹን እየሰራ ሲሆን በአፍሪካ ግብፅን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የስዕል አውደርዕዮችን አቅርቧል፡፡ የአዲስ አድማስ ወዳጅ የሆነው ሠዓሊ ዘርአዳዊት አባተ፤ ጋዜጣችን 10ኛ ዓመቱን ሲያከብር የማስታወሻ ስዕል በስጦታ ያበረከተ ሲሆን ባለፈው ሰኞ በብሔራዊ ትያትር አዳራሽ በተከበረው የአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት በዓል ዝግጅት ላይም ተጨማሪ የስዕል ስጦታ አበርክቷል፡፡ ሰዓሊው ከጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር የአፍታ ቆይታ አድርጓል፡፡

ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር እንዴት ተዋወቅህ?
ከአዲስ አድማስ ጋር የተዋወቅሁት በ1998 ዓ.ም በፀጋዬ ገ/መድህን ግጥሞች ላይ “እሳት ወይ አበባ” በሚል ርዕስ ሂልተን ሆቴል ኤግዚቢሽን ሳቀርብ አዲስ አድማስ እንዲዘግብልኝ ጠይቄ በሙሉ ፈቃደኝነት ጥሩ የሆነ ዘገባ ባወጣልኝ ጊዜ ነበር፡፡  ይህ አንዱ የቅርበታችንና የትውውቃችን መሰረት ቢሆንም እኔ ከድሮም ጋዜጣውን እወደዋለሁ፡፡ የሥነ ፅሁፍ አፍቃሪ  ስለሆንኩ ጋዜጣውን በጣም ነው የማደንቀው፡፡
የስዕል ስራዎችህን ለጋዜጣው በስጦታ ለማበርከት ያነሳሳህ ምንድን ነው?
የስዕል ስራዎቼን ለማበርከት የፈለግሁት ለሌሎች ሰአሊዎች አርአያ ለመሆን ነው፡፡ እንደዚህ ላሉ ሃገሪቷን በጥሩ ስሜት ለሚያገለግሉ የስነ ጥበብ አክባሪ የጋዜጣ ድርጅቶች የስዕል ስራቸውን ቢያበረክቱ መልካም ነው፡፡ እኔም ሁልጊዜ ከመሸጥ ማበርከትም መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የ10ኛ ዓመቱ ላይ ያበረከትኩት አድናቆቴን ለመግለፅ ነው፡፡ አሁን 15ኛ አመት ላይ ደግሞ ከአድናቆትም በላይ ለሰአሊዎች አርአያ ለመሆን ነው፡፡ በአዳራሹ ውስጥ በጣም ብዙ ሰአሊዎች ነበሩ፡፡ ስዕል ላበረክት ነው ስላቸው እየቀለዱብኝ፤ “አንተ ከዚህ ጋዜጣ ጋር የተለየ ግንኙነት ነው ያለህ” እያሉ ነበር፤ ነገር ግን ጥሩ ስሜት እንደጫርኩባቸው ይገባኛል፡፡ በ15ኛ ዓመቱ ላይ ይህን የስዕል ስራዬን በማበርከቴም ደስታ ይሰማኛል፡፡ ለ20ኛ ዓመቱም እድሜና ጤና ከሰጠኝ ማበርከቴ አይቀርም፡፡ አዲስ አድማስ በአሉን ባከበረ ቁጥር የስዕል ስጦታውን አላቋርጥም፤ እቀጥላለሁ፡፡
ከአዲስ አድማስ የትኞቹ አምዶች ይበልጥ ይስቡሃል?
አንዱ ኪነ ጥበብ ላይ አትኩሮ የሚሰራቸው ዘገባዎቹ ሲሆን ቀደም ሲል ሳይንስና ቴክኖሎጂ በሚል አምድ የሚያቀርባቸው ጥሩ ፅሁፎች ነበሩ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በየሳምንቱ የሚወጡት ትናንሽ ግጥሞች ናቸው፡፡ ሌላው በጣም የማደንቀው ገጣሚ ነቢይ የሚፅፈውን ርዕሰ አንቀፅ ነው፡፡ በተረት አዋዝቶ ስለሚፅፍ ትላልቅ መልእክት አላቸው፡፡ ከ10ኛው አመት ጀምሮ የተፃፉትን ርዕሰ አንቀፆች በሙሉ ኮምፒውተሬ ውስጥ ፋይል አድርጌ አስቀምጫቸዋለሁ፡፡ በታሪካዊ እውነቶች ላይ የተፃፉ አንዳንድ የጋዜጣው ፅሁፎች ለስዕሎቼ መነሻ ሆነውኛል፡፡
ምን አይነት የአሳሳል ዘይቤ ነው የምትከተለው?
 ሪያሊስቲክ ላይ ነው የማተኩረው ግን አብስትራክትም መስራት ጀምሬአለሁ፡፡ ሮማንቲዝምም ደስ ይለኛል፤ ላንድ ስኬፕ ደግሞ በጣም እወዳለሁ፡፡
የስዕል ስራዎችህን ከኢትዮጵያ ውጪ ያቀረብክበት አጋጣሚ አለ?
እንግዲህ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርት ስኩል በ1981 ዓ.ም በማዕረግ ነው የተመረቅሁት፡፡ የመመረቂያ ስራዬ የሚያዚያ 27 የድል ቀን ማስታወሻ ስዕል ነው፡፡ ይህን ስዕል ብዙ ጊዜ በኤግዚቢሽን አቅርቤዋለሁ፡፡ በጊዜው አድናቆት የተቸረው ነው፤ አሁን አርት ስኩል ነው ያለው፡፡ ኮፒው ደግሞ አርበኞች ማህበርን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ይገኛል፡፡ ከ20 ዓመት በላይ በስዕል ስራ ላይ የቆየሁ ሲሆን በግብፅ፣ በናይሮቢ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ኤግዚቢሽኖችን አሳይቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ወደ አውሮፓ አቀናለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡
ስለጋዜጣው የምትሰጠው አስተያየት ይኖራል?
የአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት በአል በጣም ቆንጆ ነበር፡፡ በተረፈ ጋዜጣዋ በየጊዜው መሻሻል አለባት፡፡ መጽሄትም ብትጀምሩ ጥሩ ነው፡፡ ለጋዜጣው አምዶች ቢጨመሩ… በተለይ ያልተነኩና አዳዲስ ጉዳዮችን የሚዳስሱ አምዶች መኖር አለባቸው፡፡

Published in ህብረተሰብ

አቶ ደስታ አስፋው
(በኢህአዴግ ፅ/ቤት የህዝብና ውጭ
ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ)
         አዲስ አድማስ ጋዜጣ በቆየባቸው 15 ዓመታት ውስጥ ጠንካራም ደካማም ጎኖች እንዳሉት ታዝቤያለሁ፡፡ ከጠንካራ ጎኖቹ መካከል የተለያዩ ጉዳዮችን በተከታታይ በመረጃ መልክ ለህዝብ ማድረሱ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ አልፎ አልፎ የሚዛናዊነት ችግሮች ይታዩበታል፡፡ አዲስ አድማስ አሁን የደረሰበትን ደረጃ አይቶ፣ ጥንካሬዎቹን አጠንክሮ ጉድለቶቹን አርሞ ከቀጠለ፣ለሃገራችን የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በግሌ ቢያንስ በመሰረታዊ የሙያው መርሆች ይሰራሉ ከምላቸው ጋዜጦች ውስጥ አስገባዋለሁ፡፡ አዲስ አድማስ የሚዲያ ሥራ በባህሪው የሚያጋጥመውን ተግዳሮት ተወጥቶ በየጊዜው ራሱን እያሳደገ፣ እዚህ መድረሱ ጥሩ ነው፤ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ትልቁ ነገር ግን፣ ለህዝቡ መረጃ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት የጋዜጠኝነትን መርህ መለኪያ ማድረግ ነው፡፡ የተሰሩ ጥሩ ነገሮችንም መዘገብ አለባችሁ፡፡ ለወደፊትም ጋዜጣው ደካማ ጎኑን አርሞ ጠንካራ ጎኑን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ እንኳን ለ15ኛ አመታችሁ አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡  

Published in ህብረተሰብ
Monday, 16 March 2015 09:32

‘የዲዮጋን ፋኖስ…’

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…የዘንድሮ የወሬ ነገር በጣም አስቸጋሪ አልሆነባችሁም! አለ አይደል…ከአንደበት የወጣውም፣ ከአንደበት ያልወጣውም አንድ ሺህ አንድ ቦታ ‘እየተከተፈ’… “ሁለተኛ አንዲት ነገር እንኳን ትንፍሽ ብል!...” የምንልበት ዘመን እየደረስን ነው፡፡
ስሙኝማ…አንዳንድ ጊዜ ያ ዲዮጋን የሚሉት ፈላስፋ… አለ አይደል… በገበያ መሀል ፋኖስ ይዞ “ሰው እየፈለግሁ ነው…” ያለው ነገር… “ይሄ ሰውዬ ዘንድሮ እኛ መሀል ቢኖር ምን ይለን ነበር!” አያሰኛችሁም?
የእኛው ታላቅ ሰውም…
ዓይኔን ሰው አማረው፣ ዓይኔን ሰው አማረው
የሰው ያለህ የሰው
ብለውን የለ! ሰው በበዛበት “የሰው ያለህ የሰው…” ከማለት ያድነንማ፡፡
ለምሳሌ… አለ አይደል… ሆዳችሁን እንደመቁረጥ ነገር ያደርጋችኋል፡፡ (የምር ግን… ዘንድሮ ወይ ሆዱን ቆረጥ፣ ወይ ራሱን ፈለጥ፣ ወይ ጎኑን ወጋ የማያደርገው ሰው ማግኘት አስቸጋሪ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የከተማችንን ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች ማየት ነው!)
እናላችሁ… ሰዎች “ትንሽ እንቀማመስ እንዴ!” ሲሏችሁ…
“ሆዴን ትንሽ አመም አድርጎኛል…” ትላላችሁ፡፡ ከዛላችሁ አንዱ…
“ምንህን ነው ያመመህ?” ይላችኋል፡፡
“ሆዴን ነው ትንሽ ቆረጥ ያደረገኝ…” ትላላችሁ። እሱዬው…
“ጨጓራ ምናምን አለብህ እንዴ!” ይላል፡፡
“አይ ጨጓራ እንኳን የለብኝም፣” ትላላችሁ፡፡
“ትንሽ አንጀትህ ቆስሎ ይሆናል…” ይላችኋል፡፡ በሆዳችሁ… ‘ሰውየው ምን ነካው…’ ብላችሁ ሳታበቁ… “እንደውም እኮ ሳይህ እዚህ ጉንጭህ አካባቢ ወየብ ሲልብኝ ይሄ ሰው አንጀቱን ሳያመው አልቀረም ብዬ ነበር፣” ይላችኋል፡፡
እንዴት ነው ነገሩ…እኔ የምለው… የአንድ ሰው የጤንነት ሁኔታ እኮ በጣም ግላዊ ነገር ነው፡፡ ምንህን ነው ያመመህ የሚል ነገር ለመደብንና እንለዋለን እንጂ… የሆነ ልክ ያልሆነ ነገር አለው፡፡
ይቺን የሆነ ቦታ ያነበብኳትን ስሙኝማ…ሰውየው ለጓደኞቹ ሲያወራ ነው… “ወንድሜ ታመመና ዶክተር ስሚዝን ጠራነው፡፡ ወንድሜ እሱ ያዘዘለትን መድኃኒት ወሰደና ባሰበት፡፡ እንደገና ዶክተር ጆንስን ጠራነውና ወንድሜ እሱም ያዘዘውን መድኃኒት ወስዶ አሁንም ባሰበት፡፡ አይ፣ ሊያበቃለት ነው አልንና ዶክተር ጆርጅን ጠራነው፡፡ እሱ ሥራ በዝቶበት ስለነበር ሳይመጣ ቀረ፣ ወንድሜም ተሻለው፡፡”
“ዶክተሩ  ባለመምጣቱ ተሻለኝ…” ከማለት ያድነንማ፡፡ አንዳንድ ጊዜ አራት ዶክተር ዘንድ ሄደን የአንዱ የምርመራ ውጤት ከሌላው ጋር አልገጥም ሲለን እንዲህ ብንል አይበዛብንም፡፡
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ችግሩ ምን መሰላችሁ… የሚያማችሁን “ሀኪሙ ጨጓራህ ተልጧል አለኝ…” ብላችሁ ከተናገራችሁ በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ ስለራሳችሁ ህመም ‘አዳዲስ መረጃዎች’ ይደርሷችኋል፡፡
“ተሻለህ? አንጀቱ ቆስሎ እየተሰቃየ ነው ብለውኝ…?”
“አንተ፣ የጨጓራ አልሰር እንዳለብህ ሳትነግረኝ ከሌላ ሰው ልስማ!…”
“የምንድነው ካንሰር ይዞታል ብለውኝ… ምንህን ነው ያመመህ?”
እናላችሁ…የእናንተ ህመም የከተማው ሰበር ወሬ ሆኖ ይከርምላችኋል፡፡
ህመም የዶክተሩና የበሽተኛው ምስጢር መሆኑ ቀርቶ ‘የጋራ አጀንዳ’ ሲሆን…አለ አይደል… የዲዮጋን ፋኖስ የማይመጣባችሁሳ!
የሀኪም ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ…ዶክተሩ ለበሽተኛው… “እየተሻለህ ነው፡፡ ግራ እግርህ አብጧል፣ እኔን ግን አያሳስበኝም…” ይለዋል። በሽተኛው ብሽቅ ብሎ ምን ቢለው ጥሩ ነው… “ዶክተር የአንተም ግራ እግር ቢያብጥ ኖሮ እኔም አያሳስበኝም ነበር፣” ብሎት አረፈ፡፡
ሰው በበዛበት “የሰው ያለህ የሰው…” ከማለት ያድነንማ፡፡
ሰውየው ከሚስቱ ጋር መጠነኛ ግጭት ይገጥመዋል፡፡ አለ አይደል… ‘ጭር ሲል’ ሁለቱ መልሰው የሚስማሙበት አይነት ችግር፡፡ ግንላችሁ… በሆነ መንገድ “ተኳርፈዋል…” የሚል ወሬ አንዳችን ጆሮ ውስጥ ጥልቅ የለ… ምን አለፋችሁ…ልክ እንደ አጭር ልብ ወለድ ውድድር ሁላችንም የየራሳችንን ታሪክ እንጽፍና ለሚሰማ ጆሮ ሁሉ እንነግራለን፡፡ ባልና ሚስቱም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ራሳቸው እንኳን ስለረሱት ግጭት አዳዲስ መረጃዎች ይደርሷቸዋል፡፡
“እናንተ፣ እንዲህ አገር ሰምቶ ጉድ እስኪል ስትጋጩ ምነው ያልነገራችሁን! ጨፍረን ድረን ትደብቁናላችሁ!” (አይደለም አገር ሊሰማ… ጓዳ የነበረችው ሠራተኛቸው እንኳን አልሰማችም እኮ!)
“ስማ፣ በቃ ቆረጣችሁ ማለት ነው! ንብረት ልትካፈሉ ነው ሲሉ ሰማሁ፡፡”
“ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሷል አሉ፡፡ ይሄን ያህል ያጋጫችሁ ምንድነው?”
“የት ይደርስ የተባለ ትዳር እንዲህ ይሁን!”
ምን አለፋችሁ… ማታ ‘እነሆ በረከት’ መፍትሄ የሚበጅላት ኩርፊያ የከተማው መነጋገሪያ አጄንዳ ሆና ትከርምላችኋለች፡፡
የባልና ሚስት የጓዳ ነገር የእነሱ ምስጢር መሆኑ ቀርቶ ‘የጋራ አጀንዳ’ ሲሆን…አለ አይደል…የዲዮጋን ፋኖስ የማይመጣባችሁሳ!
ሰው በበዛበት “የሰው ያለህ የሰው…” ከማለት ያድነንማ፡፡
(ስሙኝማ…እግረ መንገዴን… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እዛ አማሪካን ውስጥ በ‘ቫለንታይን ዴይ’ ሰሞን የፍቺ ጥያቄ አርባ በመቶ ያድጋል የሚል ነገር አነበብን፡፡ የእኛ አገር ‘ጥሬ ሀቅ’ ይነገረንማ፡፡)
እናላችሁ…የተባለውም፣ ያልተባለውም እየተከተፈና እየተመነዘረ ነገሮች ሲጣመሙ ሰዋችን “መታፈር በከንፈር” ቢል አይገርምም፡፡ አንዳንድ ሰዎች… አለ አይደል… በመልስና በቅጣት ምት መካከል ያለውን ልዩነት እንኳን ሳያውቁ ስለ ‘አርሴና ማንቼ’ የሚያወሩት ሌላ ‘ቁም ነገር’ አጥተው አይደለም፡፡ ስለ አርሴና ማንቼ ማውራቱ በምንም መንገድ ለመጠምዘዝ አይመችማ! “ስማ እሱ ሰውዬ እኮ ያለውን ሰማህ! ሩኒን የሚስተካከለው የለም አለ አሉ፡፡ እኔ ከእነ….እንትና ጋር በህቡእ እንደሚሠራ እጠረጥረዋለሁ…” ምናምን አይባልማ፡፡
እሰየው ነው…ቢያንስ፣ ቢያንስ እስካሁን የአርሴና የማንቼ ነገር ከራሳችን ጉዳይ ጋር አያይዞ ለመፈረጅ አያመችማ!
እግረ መንገዴን…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…በቀደም አንዱ ወዳጃችንን ብዙም የማይቀርበው የሰፈር ሰው ሰላም ይለዋል፡፡ የሚሰማውን ከመናገር ወደኋላ የማይለው ወዳጃችን ደንገጥ ቢልም በበኩሉ ሰላም ይላል፡፡ ከዛማ ሰውየው ምን ቢለው ጥሩ ነው…“ማንን ነው የምትመርጠው?” ወዳጃችንም ሰውየው ምን እንደሚያወራ መጀመሪያ ግራ ገብቶት ነበር፡፡ በኋላ ነገሩን ሲረዳ ምን አለው መሰላችሁ…“ምን አገባህ!” አለው፡፡ አሪፍ አይደል! እናላችሁ… “ምን አገባህ!” ልንባል የሚገባን ሰዎች እየበዛን ሳንሆን አንቀርም፡፡
ምንም ነገር የመምረጥና ያለመምረጥ ጉዳይ የራሳችን የግል ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የማያገባው ዘው ሲልበት…አለ አይደል…የዲዮጋን ፋኖስ የማይመጣባችሁሳ!
ሰው በበዛበት “የሰው ያለህ የሰው…” ከማለት ያድነንማ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Monday, 16 March 2015 09:32

የአትሌቶቻችን ህንፃዎች

በሩጫው የተሳካላቸው አትሌቶች የዕውቁን አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴን አርአያነት በመከተል ጥሪታቸውን በኢንቨስትመንት ላይ እያፈሰሱ ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹም በሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ላይ በማተኮር ትላልቅ ህንፃዎችን ገንብተዋል፡፡ አትሌቶች በስፖርት እና በኢንቨስትመንት በተያያዘ ያላቸው ካፒታል ከ7 እስከ 10 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት መረጃዎች ይገልፃሉ። ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል እንዲሁም ማራቶን ኢንጅነሪንግ ባለፈው ዓመት ብቻ  እስከ 28 ሚሊዮን ብር የገቢ ቀረጥ መክፈላቸውን ያመለከቱ መረጃዎችን በመንተራስ ለመገንዘብ የሚቻለው በሁሉም አትሌቶች እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኢንቨስትመንቶች ለመንግስት በሚያስገቡት የቀረጥ ገቢ ምን ያህል ሚና እንዳላቸው ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች  በወርቅ ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያን ሲያኮሩ የቆዩት  አትሌቶች ካለፉት 10 ዓመታት  ወዲህ ደግሞ በኢንቨስትመንት ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ አገራቸውን  የሚያለሙ ባለውለተኞች ሆነዋል።  አትሌቶች የተሠማሩባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች በሪል ስቴት፣ በወጭና ገቢ ንግድ፣ በሆቴል፣ በስፖርትና በግብርና፣ በአውቶሞቲቭ፤ በእርሻ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ኢንቨስትመንቶቻቸው እስከ ሶስት ሺ ለሚደርሱ ኢትዮጵያውያንም የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ አትሌቶቹ ለህንፃዎቻቸው ግንባታ በተለይ መገናኛና ቦሌን የመረጡ ይመስላሉ፡፡
በመገናኛ እስካሁን አምስት የአትሌቶች ህንፃዎች እየተገነቡና ስራ እየጀመሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባና ስለሺ ስህን ንብረት የሆነው “ስለሺ ስህን ቢዝነስ ሴንተር” ተጠቃሽ ነው፡፡ ይሄ ህንፃ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ጥንዶቹ አትሌቶች በቀድሞው ካራማራ ሆቴል አካባቢ ባለ18 ፎቅ ህንፃ አራት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት እቅድ ይዘዋል፡፡ እዚያው መገናኛ ላይ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ከሁሉም አትሌቶች በትልቅነቱ ግንባር ቀደም የሆነ ባለ 15 ፎቅ ህንፃ እየገነባች ነው፡፡ በሪል እስቴት ዘርፍ የተሰማራችው ደራርቱ በአሰላና አዳማም ህንፃዎችን ገንብታለች፡፡  በመገናኛ አካባቢ በግንባታ ላይ ካሉት ህንፃዎች አንዱ የገዛሐኝ አበራ ነው፡፡ በሃዋሳ ከ342 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት  ሪዞርት ያስገነባው ገዛሐኝ አበራ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሆቴሌቹን የሚገነባ እና በሪል ስቴት እና በእርሻ ለመስራት የሚንቀሳቀስ ሆኗል፡፡ ሌላዋ መገናኛ አካባቢ ህንፃ እያስገነባች ያለችው አትሌት ደግሞ መሰረት ደፋር ናት፡፡
ቦሌ አካባቢ ህንፃ በመገንባት ፈርቀዳጅ የሆነው አትሌት ኃይሌ ሲሆን ፤ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከ10 በላይ ህንፃዎች አሉት፡፡ ኃይሌ በመጀመርያ ያስገነባው ዓለም ሲኒማ ያለበትን ሃይሌ ዓለም ህንፃ ነው፡፡ በዚያው በቦሌ አካባቢ በመድሃኒያለም ቤተክርስትያን አቅራቢያም አትሌቶች በርካታ ህንፃዎችን ገንብተው ስራ ጀምረዋል፤ እየገነቡም  ናቸው፡፡የአትሌት ቀነኒሳ ሆቴል ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው፡፡የቀነኒሳ ሆቴል ባለአራት ኮከብ ሲሆን በኢጣሊያዊ አርክቴክት ዲዛይኑ ተሰርቶ በ200 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባ ነው፡፡ ከአትሌት ኃይሌ በመቀጠል ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ የሚታወቀው አትሌት ቀነኒሳ፤ እስካሁን 500 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት አድርጓል፡፡ አትሌቱ ከ”ቀነኒሳ” ሆቴል ባሻገር በሱልልታ የአትሌቲክስ ማእከልና ሆቴል  ከማስገንባቱም በላይ በአሰላና በትውልድ ከተማው በቆጂም ህንፃዎችን ሰርቷል፡፡ በሩጫ ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማቶች በመሰብሰብ ከዓለም ሴት አትሌቶች በ6ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አትሌት ብርሃኔ አደሬም ቦሌ መድሃኒያለም አካባቢ ከሌሎቹ ገዝፎ የሚታይ እና “ብርሃን አፍሪካ” የተባለ ባለ 8 ፎቅ ህንፃ አስገንብታ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ እዚያው አካባቢ በግንባታ ላይ የሚገኘው ሌላው ባለ 10 ፎቅ ህንፃ የአትሌት ገብረእግዚአብሄር ነው፡ አትሌት ገብረእግዚአብሄርና ባለቤቱ ወርቅነሽ ኪዳኔ ሌሎች ሁለት ህንፃዎችን በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች እያስገነቡም ይገኛሉ፡፡ ጌጤ ዋሚ በትውልድ ስፍራዋ ደብረብርሃን ሆቴል የምታስተዳድር ሲሆን አንጋፋው አትሌት ወርቁ ቢቂላ በዱከም ካለው መለስተኛ ሆቴል በተጨማሪ በምስራቅ አፍሪካ በውሃ ጉድጓድ ቁፋሮዎች በርካታ ፕሮጀክት የሚያቀሳቅስ ኩባንያን ከሆላንድ አጋሮቹ ጋር እያከናወነ ይገኛል፡፡ ሌላው አትሌት  በላይ ወላሼ  በቡና ኢንቨስትመንት የሚንቀሳቀስ ሲሆን  ሌሎች እውቅ  እና ወጣት አትሌቶችም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እና የንግድ ስራዎች መሰማራታቸው ይገለፃል፡፡ ዜግነታቸውን ለውጠው ለውጭ አገራት የሚሮጡ አትሌቶችም መገናኛ አካባቢ ህንፃ ገንብተዋል፡፡ ለባህሬን የምትሮጠው ማርያም ዩሱፍ ጀማል፤ የካ ጋራ ላይ በ200 ሚሊዮን ብር “ቤልቪው” የተባለ ሆቴል ገንብታለች፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች በስፖርቱ ኢንቨስትመንት መስክም ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ሱሉልታ የሚገኘው “ያያ ቪሌጅ” በአንድ የቀድሞ አትሌትና በኃይሌ ገብረስላሴ ሽርክና የተገነባ ነው፡፡ እዚያው ሱልልታ የቀነኒሳ የአትሌቲክስ ማእከልና መዝናኛም ይገኛል፡፡ በሱልልታ የተገነባው የቀነኒሳ የስፖርት ማእከል የመሮጫ ትራክ፤ የጎልፍ ሜዳ፤ የቅርጫት ኳስ እና የእጅ ኳስ ሜዳዎች ያሉትና የተለያዩ የመዝናኛ አገልግሎቶች በመስጠት እስከ 120 ሰዎች የሚያስተናግድ ሆኖ በ350 ሚሊዮን ብር የተገነባ ነው፡፡ አትሌቶች የሩጫ ውድድሮችን በማስተናገድ ዘርፍም ኢንቨስት እያደረጉ ነው፡፡ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው ከ14 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውና ከ100 ውድድሮች በላይ ያዘጋጀው የኃይሌ ገብረስላሴ “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ አትሌት ገብረስላሴ “የተራራ ላይ ሩጫ” በሚል ተመሳሳይ ኢንቨስትመንት ውስጥ ገብቷል፡፡

Page 10 of 21