በደራሲና ዳይሬክተር ሄርሞን ሃይላይ የተዘጋጀውና በእንግሊዛዊው ማክስ ኮኔል ፕሮዲዩስ የተደረገው “የፍቅር ዋጋው” የተሰኘ ፊልም፤ ነገ በሁሉም የግል ሲኒማ ቤቶች በተመሳሳይ ሰዓት እንደሚመረቅ አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ ላለፉት 47 ዓመታት የፊልም ፌስቲቫል ሲያዘጋጅ በቆየውና ቡርኪናፋሶ በሚገኘው “ፌስ ባኮ” የፊልም ፌስቲቫል ላይ ተወዳድሮ ሰሞኑን እንዳሸነፈ የተነገረለት ፊልሙ፤ የ1፡39 ርዝማኔ ሲኖረው ሮማንስ ኮሜዲ ዘውግ እንዳለውና በፍቅር ጉዳይ ላይ እንደሚያጠነጥን ታውቋል፡፡ በፊልሙ ላይ እስክንድር ታምሩ፣ ፍሬወይኒ ገብረጊዮርጊስና ሌሎችም ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡  

Saturday, 21 March 2015 10:38

በሩን ክፈቱልኝ

(በአዲስ አድማስ የ15ኛ ዓመት የሥነፅሁፍ ውድድር፤ 3ኛ የወጣው አጭር ልብወለድ)

እንባ
ማን እንደነገረኝ አላውቅም ወይም የት እንዳነበብኩት ትዝ አይለኝም፡፡ የሴት ልጅ ታላቁ ወዳጇ እና መደበቂያዋ እንባዋ ነው አሉ፡፡ ሁሏም ሴት አልቃሻ ላትሆን ትችላለች፤ እኔ ግን ነኝ፡፡ ለኔ እንባዬ ብዙ ነገሬ ነው፡፡ ጥቃቴን የተወጣሁበት፤ ሀሳቤን የከፈልኩበት፤ ጭንቀቴን ያቃለልኩበት እንባዬ ብቻ ነው፡፡ በህይወቴ የመጀመሪያ ምርር ያለ ለቅሶ ያለቀስኩት የአባቴ ቀብር ላይ ነበር፡፡ ሁለተኛውን መራር ለቅሶ ያለቀስኩት ደግሞ እዚያች ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ ያ ክፍል ዛሬም ይታየኛል። ግርግዳው ውሃ ሰማያዊ ቀለም ተቀብቷል፡፡ በሩ ግራጫ ቀለም ያለው የብረት በር ነበር፡፡ ክፍሉ ውስጥ ሰፋ ያለ አልጋ አለ፡፡ አልጋው መሃል ላይ ኩርምት ብዬ ስቀመጥ በቀኜ በኩል አነስ ያለች ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ ግራጫማ ቴፕ ሪከርደር አለ፡፡ ከጠረጴዛዋ ስር የተለያዩ መፅሄቶችና ጋዜጦች ይታዩኛል፡፡ በግራዬ በኩል ደግሞ ሁለት ተካፋች በር ያለው ቡናማ ቁምሳጥን አለ፡፡ ከቁምሳጥኑ ላይ አንድ ከፍ ያለ ሻንጣ አለ፡፡ ክፍሉ ውስጥ የማስታውሳቸው እቃዎች እነዚህ ናቸው፡፡
ተመራማሪዎች ከሰውነታችን ስልሳ ፐርሰንቱ ውሃ ነው ይላሉ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይሄ ነገር እውነት ነው፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮማ እዚያች ክፍል ውስጥ ሊያውም ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ያንን ሁሉ እንባ ከየት አምጥቼ አነባው ነበር፡፡ ጥር 10/1994 ዓ.ም ያስተዋወቀኝ ታላቁ ወዳጄ እንባዬ ነው፡፡ እንባዬ ጉንጬን ብቻ ሳይሆን ደሜን አጥቦልኛል፡፡ አቅም አልነበረኝም፡፡ ሲመቱኝ መልሼ የምመታበት፤ ሲያጠቁኝ የምመክትበት አቅም አልነበረኝም። ስለዚህ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ ማንንም ሴት ጠይቁ። እንባ ስሜትን ያቃልላል፡፡ እንባ የታመቀ ቁጭትን ያረግባል፡፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ እንባዬ አብሮኝ አለ፡፡ አሁንም ትዝ ሲለኝ አለቅሳለሁ፡፡
ዛሬ
እኔ ሰናይት ሀይሉ ዛሬ ሃያ ዘጠኝ ዓመት ሞላኝ። ዛሬ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በህንፃ ምህንድስና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተቀብያለሁ፡፡ የማስተርስ ዲግሪዬን በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ አግኝቻለሁ፡፡ በግል የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ተቀጥሬ እሰራ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ከሁለት ጓደኞቼ ጋር የራሳችንን የኮንስትራክሽን ድርጅተ ለመክፈት እየተሯሯጥን ነው፡፡ ስፖርት እወዳለሁ፡፡ ዛሬ በወርልድ ቴኳንዶ ቀይ ቀበቶ ይዣለሁ፡፡ የማንቼ ቀንደኛ ደጋፊ ነኝ። ደቪድ ቤካምን ከልቤ እወደው ነበር፡፡ እርሱን ለማየት የማንቼ ጨዋታዎችን መከታተል ጀመርኩ እና በዚያው ተለክፌ ቀረሁ፡፡ ዛሬ እናቴን የምጦረው ቤቱን የማስተዳድረው እኔ ነኝ፡፡ ዛሬም ግን ልቤ እዚያው ክፍል ነው፡፡ ትንፋሻቸው ይቀረናኛል፤ የላባቸው ጠረን ይሸተኛል፤ በኔ ስቃይ ያገኙት ወሲባዊ ደስታ ትዝ ይለኛል፡፡ ዛሬም በሶስት ጎረምሶች የተደፈረች የአስራ ስድስት ዓመት ልጅ ነኝ፡፡ አይኔን መጨፈን ብቻ ወደዚያ ክፍል መልሶ ያስገባኛል፡፡ ዛሬም እፈራለሁ፡፡ ዛሬም እበረግጋለሁ፡፡
ወንድ  
ለእኔ ወንድ በሁለት ይከፈላል፡፡ ከወገቡ በላይ እና ከወገቡ በታች፡፡ ከወገብ በላይ ማለት ልቡ፤ መንፈሱ እና ነፍሱ ያለበት ቦታ ነው፡፡ ከወገቡ በታች ደግሞ አውሬነቴ ያለበት ቦታ ማለት ነው፡፡ ያን ቀን ሶስቱም ከወገብ በላይ ሙታን ነበሩ፡፡ በህይወት ያለው የሚያስበው እና የሚንቀሳቀሰው ከወገባቸው በታች ያለው ማንነታቸው ነበር፡፡ ነፍሱ ከራሱ ጋር ያለ ሰው እንደዚያ አውሬ አይሆንም፡፡ እናት ያለው፣ እህት ያለው እንደዚያ አይጨክንም፡፡
ከዚያች ቀን በፊት ወንድን የማውቀው ከወገቡ በላይ ነበር፡፡ ለምሳሌ ኤልያስ ሳህሉ፡፡ ኤልያስ የልጅነት ጓደኛዬ ነው፡፡ አንድ ግቢ ነበር የምንኖረው። እስከ አስራ አራት ዓመቴ ድረስ የማንነጣጠል ጓደኛሞች ነበርን፡፡ ያደግነው ጥቁር አንበሳ አካባቢ ወይም ሜትሮሎጂ አጠገብ ካለው የኪራይ ቤቶች አፓርትመንት ነበር፡፡ የነሱ ቤት ሁለተኛ ፎቅ ላይ፣ የኛ ቤት ደግ ሶስተኛ ፎቅ ላይ ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት እየሄድኩ አንዳንዴ ከኤልያስ ጋር አብረን እናጠናለን፡፡ ከግቢው ልጆች ጋር ስንጫወት ከመቱኝ ወይም ካናደዱኝ ስለእኔ ይከራከርልኝ ይጣላልኝ ነበር፡፡ በጣም ልጆች ሆነን ደግሞ እቃ እቃ ስንጫወት እርሱ ባል፣ እኔ ደግሞ ሚስት እንሆን ነበር፡፡ የእቃ እቃ ሰርጋችን ላይ እጄን ይይዘኝና እንደሙሽራ ቀስ እያልን ስንራመድ፣ ሌሎቹ ልጆች ሙሽራዬ ይሉልን ነበር፡፡ የእሱ ቤተሰቦች ቤት ሰርተው ንፋስ ስልክ አካባቢ ገቡና ተረሳሳን፡፡ እኔ ወንድን ከዚያች ቀን በፊት ከወገቡ በላይ ነበር የማውቀው፡፡
ያን ቀን ግን የማላውቀውን የወንድ ማንነት እንዳውቅ ተገደድኩ፡፡ ወንድ ከወገቡ በታች አውሬ ነው፡፡ ለቅሶ የማያግደው፤ እንቢታ የማያቆመው፤ ጩኸት ግድ የማይሰጠው፤ ደም የማያራራው አውሬ!!!
አልጋ ልብስ
አልጋ ልብሱ ደማቅ አረንጓዴ ነበር፡፡ እዚያች ክፍል ውስጥ የደረሰብኝን ስቃይ የምናውቀው እኔ፤ ሶስት ወንዶች እና ያ አረንጓዴ አልጋ ልብስ ነን፡፡ ያ አረንጓዴ አልጋ ልብስ በደሜ ተጨማልቋል፡፡ ያ አረንጓዴ አልጋ ልብስ በሶስት ወንዶች የዘር ፍሬ ላብ ረጥቧል፡፡ ያ አረንጓዴ አልጋ ልብስ በእንባዬ ርሷል። እነዚያን አውሬዎች ብከሳቸው ኖሮ አንደኛ ምስክር አድርጌ የምጠራው ያንን ባለውለታዬን አረንጓዴ አልጋ ልብስ ነበር፡፡ በመደፈሩ መካከል ወይም አንዱ ደፋሪዬ ወጥቶ ሌላው እስኪተካ ድረስ ሰውነቴን እሸፍንበት ነበር፡፡ አለም በጨከነብኝ ጊዜ እርቃኔን ሸፍኜበታለሁ፡፡
መደፈሬን ለማንም አልተናገርኩም፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ለማን ይወራል? ያን ቀን ተደብቄ ነበር እዚያ ፓርቲ ላይ የተገኘሁት፡፡ አድሬና አምሽቼ  ስመጣ እናቴ በጣም ተቆጣችኝ፡፡ እያነከስኩ መምጣቴ እንዳይታወቅብኝ ተጠንቅቄ ወደ መኝታ ቤቴ ገብቼ ተኛሁ፡፡ ለሳምንት ያህል ሽንት ቤት መጠቀምና ሽንቴን መሽናት ለኔ ስቃይ ነበር፡፡ ለእናቴ አልነገርኳትም፡፡ የቤቱ ብቸኛ ልጅ ስለሆንኩ ሌላ የምነግረው ሰው አልነበረም፡፡ ለትምህርት ቤት ሴት ጓደኞቼ እንዲህ ሆንኩ ብዬ መናገሩ ደግሞ የድንጋይ ያህል ከበደኝ፡፡ ለመደፈሬ እራሴንም ጥፋተኛ አደርጋለሁ፡፡ እዚያ ፓርቲ መሄድ አልነበረብኝም፡፡ የሰጡኝንም መጠጥ መጠጣት አልነበረብኝም፡፡
ሙሽራ ቀሚስ
ከልጅነቴ ጀምሮ ሙሽራ ቀሚስ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ስድስት አመቴ እያለ አክስቴ ለምለም ስታገባ ሻማ ያዥ ነበርኩ፡፡ ያኔ ታዲያ እሷ የለበሰችውን የሙሽራ ቀሚስ ውድድ አድርጌው ነበር፡፡ ንጣቱ፤ መንዠርገጉ፤ ሙሽሪትን ንግስት ማስመሰሉ ደስስስ ይላል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ አስራ ስድስት አመቴ ድረስ የሰርግ ዘፈን ስሰማ ወይም ሙሽሮችን ሳይ እራሴን በሙሽሪት ቦታ አድርጌ በሰርጌ ቀን ስለማደርገው የሙሽራ ቀሚስ አልም ነበር፡፡
“ሽነት ነይ ነይ” የሚለውን የሰርግ ዘፈን በጣም እወደው ነበር፡፡ የሰርጌ ቀን በዚህ ዘፈን ከእናትና አባቴ ጋር እስክስ እንደምንል አስብ ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል? በልጅነቴ አውሬ ሴትነቴን ቀማኝ፡፡ አባቴም በመኪና አደጋ ከመደፈሬ ሰባት ወር በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡
የዛሬ ዓመት የቅርብ ጓደኛዬ ስታገባ አንደኛ ሚዜ ነበርኩ፡፡ ለሷ የኪራይ የሙሽራ ቀሚስ እየዞርን ስንፈልግ የሙሽራ ቀሚስ ፍቅሬ ተቀሰቀሰብኝ። አንዱ ቤት በጣም የምወደው አይነት የሙሽራ ቀሚስ አየሁ፡፡ ጓደኞቼን ካለካሁት ብዬ አስቸገርኩ። ከዚያን ቀን በፊት ወንድን በፍቅር እንደማላስጠጋ፤ የመውለድ እና የማግባት ምኞት እንደሌለኝ ስለሚያውቁ ሙሽራ ቀሚስ ልልበስ ማለቴ ተአምር ነው የሆነባቸው፡፡ ልብሱ ደግሞ የክፋቱ ክፋት ልክክ አለብኝ፡፡ ያንን ቀሚስ ለብሼ መስታወት ፊት ስቆም እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡ እዚያች ክፍል ውስጥ ወድቆ ለቀረው ሴትነቴ አለቀስኩ፡፡ እኛ ቤት “ሽነት ነይ ነይ… ሽነት ነይ ነይ …የሰንዬ እናት እልል በይ” እንደማይባል ሳስብ አለቀስኩ፡፡
ስም
ሀበሻ ግን ምን ነክቶት ነው ስምን መላዕክ ያወጣዋል ብሎ የሚያስወራው? ሃሰት ነው!!! እዚያች ክፍል ውስጥ ነፍሴን ማወቅ ስጀምር ሄኖክ እላዬ ላይ ወጥቶ እራሱን እያመቻቸ ነበር። መድኀኒት ቢጤ ሰጥተውኝ ስለነበር መጀመሪያ ምን እያደረገ እንደሆነ በደንብ አልገባኝም ነበር። ባለ በሌለ ሀይሉ ክብረ ንፅህናዬን ሲገስ ግን ያኔ በደንብ ነቃሁ፡፡ ሄኖክ የመፅሐፍ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላሳመረ ወደ ሰማይ የተነጠቀ ፃድቅ ነው፡፡ ይሄኛው መላጣው ሄኖክ ደግሞ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ አራት ጊዜ በሃይል ደፍሮኝ በቁሜ ገሃነም አስገብቶኛል፡፡ ደግሞ እንዴት እንደሚስገበገብ? የተደፈርኩት የቤተሰቦቹ ቤት ውስጥ በተሰጠው ሰርቪስ ክፍል ውስጥ ነው። በእናት አባቴ ሱቅ ውስጥ አብሯቸው የሚሰራ የሃያ ሰባት አመት ጎረምሳ ነበር፡፡ ፓርቲውን ያዘጋጀው የሱ ታናሽ ወንድም ነበር፡፡
ሁለተኛ ደፋሪዬ ደግሞ ዳግም ይባላል፡፡ የሰፈራችን ልጅ ነው፡፡ በደንብ አንግባባም ነበር፡፡ እርሱ ነው “ቆይና እኔ እሸኝሻለሁ” ብሎ ከጓደኞቼ ነጥሎ አስቀርቶ ለዚህ ስቃይ የዳረገኝ፡፡ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ሶስት ጊዜ ደፍሮኛል፡፡ ሙሉ ስሙ መሆን የነበረበት ዳግማዊ ሳጥናኤል ነበር፡፡ እሱ ግን ዳግም ፍሰሃ ይባላል፡፡ ድንቄም!!!
ሶስተኛው ደፋሪዬ የፓርቲው አዘጋጅ የሄኖክ ታናሽ ወንድም አድነው ነው፡፡ እዚያች ክፍል ውስጥ ከአርብ ከምሽቱ አራት ሰዓት ገብቼ ቅዳሜ ከምሽቱ አራት ሰዓት ስወጣ አንዴ ብቻ ነው የደፈረኝ፡፡ ሳይፀፅተው አይቀርም፡፡ ወደ ቤቴ ልሄድ ስል መፀዳጃ ቤት የወሰደኝ፤ ሰፈሬ ድረስ የሸኘኝ እርሱ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ደፍሮኛል፤ ከመደፈርም አላዳነኝም፡፡
ከዚህ ነገር የምትረዱት… ስምን ፈፅሞ መላክ አያወጣውም!!!
ፆታዊ ፍቅር
በደረሰብኝ ጥቃት ምክንያት ወንድን እንደ ስራ ባልደረባ ወይም እንደ ወንድም ወይም እንደ ንፁህ ጓደኛ ካልሆነ እንደ ፍቅረኛ አላቀርብም፤ አልመኝም። ሁሉም ወንድ አንድ እንዳልሆነ ባውቅም ወንድን ማቅረብ አቃተኝ፡፡ እህ ብዬ ባላደምጣቸውም “ወደድኩሽ” ያሉኝ ወንዶች ገጥመውኛል፡፡ አላመንኳቸውም!!!
ባለፈው ዓመት ግን የማላልፈው ነገር ገጠመኝ፡፡ ኤልያስን ከአስራ ሶስት ዓመት በኋላ ቢሮዬ ለጉዳይ መጥቶ አገኘሁት፡፡ ገና ሳየው ልቤ ድንግጥ አለ፡፡ እርሱም ደስ ብሎት ሰላም አለኝ፤ ሳመኝ፡፡ ሻይ፤ ቡና፤ ማኪያቶ፤ ምሳ፤ እራት ተገባበዝን፡፡ አንድ ቀን እንዲህ አለኝ፤ “ሰሞኑን ምን እንደሆነ አላውቅም፤ ወንድ እንደምትፈሪ ገብቶኛል፡፡ የደረሰብሽ ነገር እንዳለ ያስታውቃል፡፡ ግን እኔ ወድጄሻለሁ፡፡ የልጅነቴ ነሽ፤ በፍቅር አብረሽኝ ብትሆኚ ደስ ይለኛል፡፡” በፍፁም ትህትና እንደማልፈልገው ነገርኩት፡፡ ወንድም እና እህት እንደሆንን አስረዳሁት፡፡ ሰማያዊ ግርግዳ ያለበት ክፍል አብረን ብንገባ እና ግራጫውን በር ብንዘጋ አውሬ እንደሚሆንብኝ አውቃለሁ፡፡
ግን ለምንድን ነው አብሬው ስሆን ደስ የሚለኝ? ምን ልሁን ብሎ ነው የምወዳቸውን ዘፈኖች የሚዘፍነው? ለምንድን ነው እንዲያቅፈኝ የምፈልገው? ላብድ ነው እንዴ? እርሱም እኮ ወንድ ነው!!!
ግን እርሱ ለምን አይርቀኝም? ሲደውል ካላነሳሁ ይመጣል፡፡ ፊት ስነሳው ስጦታ ገዝቶ ይመጣል። ደግሞ አንዳንዴ ይጠፋብኛል፡፡ ከዚያ ፈልጌ አገኘዋለሁ፡፡ ያኔ ደግሞ እርሱ ደስ ይለዋል። ምን አደርግለታለሁ ግን? እኔ ሙሉ ሴት አይደለሁም። የሆነ የጎደለኝ ነገር አለ፡፡ እነ ሄኖክ ያበላሹት። አረንጓዴ አልጋ ልብስ ላይ ተቆርጦ የቀረ። ከዚያ ክፍል ማነው የሚያወጣኝ? ማነው በሩን የሚከፍትልኝ?
ቅዠት
በሳምንት ሁለት ሶስቴ ቅዠት ያስቸግረኛል። የሚቀረና የወንድ ትንፋሽ፤ ግራጫ የብረት በር፤ ስግብግብ የወንድ እጆች፤ የሶስት ወንድ ጠረን፤ ሰማያዊ ግርግዳ፤ ስደፈር እቆጥረው የነበረው ጣራ፤ የማይነጋ ሌሊት፤ ከብልቴ የወጣ ደም፤ አረንጓዴ አልጋ ልብስ፤ እንባ፤ ፍራቻ… በቅዠቴ ውስጥ አሉ። አንዴ ከቃዠሁ ተመልሼ መተኛት አልችልም፡፡ ሲቆይ ሲቆይ ጋብ ብሎልኝ እንጂ መጀመሪያ ሰሞንማ በእንቅልፍ እጦት አስራ አንደኛ ክፍልን ደግሜያለሁ።
አሁን አሁን ቅዠቴ መልኩን ቀይሯል፡፡ ኤልያስ መጥቶ ከአልጋው ላይ ሲያነሳኝ፤ ከሶስቱ ጋር ስለእኔ ሲደባደብ፤ ተዋት ብሎ ለእኔ ሲከራከር ወይም ከደፋሪዎቼ ሊያድነኝ ሲሞክር ይታየኛል፡፡ ላብድ ነው እንዴ?
አባ ማርቆሬዎስ
የኤልያስ ፍቅር እያየለብኝ መጣ፡፡ ግን ደግሞ ፍቅረኛው መሆንም አቃተኝ፡፡ የንስሃ አባቴ ጋ ሄድኩና ለማንም ያልነገርኩትን ታሪኬን ነገርኳቸው። በሩን ከፍተው ከዚያች ክፍል እንዲያወጡኝ ለመንኳቸው፡ ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አፀዱ ውስጥ ተቀምጠን ተናዘዝኩላቸው፡፡ እህ ብሎ የሚያደምጥ ከተገኘ መናገር ደስ ይላል ለካ፡፡
“ወለተ ማርያም፤ መፍትሄው እኮ በእጅሽ ነው፡ እርግጥ የደረሰብሽ ነገር አሰቃቂ እንደሆነ ይገባኛል፡ እግዚያብሔር ይመስገን ላልተፈለገ እርግዝና ወይም በሽታ አለመጋለጥሽ ደስ ይላል፡፡ ግን አሁን ጊዜው ነው፡”
“ለምኑ?” አልኳቸው ግራ እንደተጋባሁ፡፡
“ይቅር ለማለት” አሉኝና እርፍ፡፡
“እኮ ደፋሪዎቼን ይቅር ልበል?”
“አዎ ልጄ፡፡ ይቅር ለእግዚአብሔር በያቸውና በሩን ከፍተሽ ውጪ፡፡ የበሩ እጀታ ከውስጥ ነው፡፡ ይቅር የምትይው ለራስሽ ነው፡፡ ከዚህ በሁዋላ የበደሉሽን በደል ይዘሽ ላለመዞር ይቅር ለእግዚአብሔር በያቸው፡፡ ዘመንሽን ሙሉ እዚያች ክፍል ተዘግቶብሽ ላለመኖር ስትይ ይቅር በያቸው፡፡
“እንዴ አባ …” አልኩ ግራ ገብቶኝ፡፡
“ይቅር ማለት ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን እርሱ ይቅር እንዳለን የበደሉንን ይቅር ማለት አለብን፡፡ እስከመቼ የነሱን ሀጥያት ይዘሽ ትዞሪያለሽ? እስከመቼ በነሱ ሀጥያት እራስሽን ትቀጫለሽ?”
ወደ መቅደሱ ሮጥኩና ተንበረከኩ፡፡ ስነሳ ኤልያስ ትዝ አለኝ፡፡ ደወልኩለት፡፡ ፊልም አብረን ልንገባ ተስማማን፡፡           

Published in ልብ-ወለድ

በቤዛ ሃይሉ ተደርሶ በመስፍን ኃይለየሱስ ዳይሬክት የተደረገው “የሃምሌ ሙሽራ” የተሰኘው ፊልም ለተመልካች መቅረብ ጀመረ፡፡ ባለፈው ሰኞ በአዶት ሲኒማና ቴአትር አዳራሽ የተመረቀው ፊልሙ፤ የ1፡35 ርዝማኔ ያለው ሲሆን ሰርቶ ለማጠናቀቅ አራት ወራትን እንደፈጀ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዶክተር ጌታቸው ተድላ አበበ ፕሮዲዩስ በተደረገው “የሐምሌ ሙሽራ” ፊልም ላይ መስፍን ኃይለየሱስ፣ ራሄል ግርማ፣ ስዩም ተፈራና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡ ፊልሙ በሁሉም የግል ሲኒማ ቤቶች እየታየ ላይ ነው ተብሏል፡፡

Saturday, 21 March 2015 10:33

የሲኒማ ጥግ

ፊልሙ ከመሰራቱ በፊት የገበያ ኃይሎች የተወሰኑ ህጎች ይጭኑበታል፡፡
አላን ሪክማን
ተዋናይ አብዛኛውን የመጀመሪያ የሙያ ዘመኑን የሚያሳልፈው ያገኘውን እየሰራ ነው፡፡
ጃክ ኒኮልሰን
እንደምተውናቸው ገፀባህሪያት ነው ብላችሁ ለአፍታም እንኳን እንዳታስቡ። አይደለሁም፡፡ ለዚያም ነው “ትወና” የተባለው፡፡
ሊኦናርዶ ዲካፕሪዮ
እያንዳንዱ የፊልም ተማሪ፤ ት/ቤት የሚገባው የራሱን ፊልም ለመፃፍና ዳይሬክት ለማድረግ በማሰብ ይመስለኛል። ያንን ለማድረግ ምን እንደሚያስፈልግ አይገነዘቡም፡፡ ሂደቱ እንዴት ያለ እንደሆነ አያውቁትም፡፡
አሌክሲስ ብሌደል
አብዛኞቹ እኔ የሰራኋቸው ፊልሞች የተበላሹት በሚሰሩ ወቅት ሳይሆን ከተሰሩ በኋላ ነው፡፡
ቼቪ ቼስ
ጥሩ ተዋናይ ከራሱ በስተቀር ማንንም መውደድ የለበትም፡፡
ዣን አኖሊህ
ራሴን እንደልብወለድ ገፀባህርይ መፍጠር እፈልግ ነበር፡፡ እናም አደረግሁት፡፡ ከዚያማ ብዙ ግራ መጋባት ፈጥሮ ነበር፡፡
ዣኔት ዊንተርሰን
ሆሊውድ ብዙ ተዋናዮችን ሳይሆን ብዙ ምስሎችን የሚቀርፁበት ስፍራ ነው፡፡
ዋልተር ዊንሼል
ማንም ሰው መሰረታውያኑን ካወቀ፣ ፊልም ዳይሬክት ማድረግ ይችላል፡፡ ፊልም ማዘጋጀት (መስራት) ተዓምር አይደለም፤ ጥበብም አይደለም፡፡ የዳይሬክቲንግ ዋናው ነገር የሰዎችን ዓይን በካሜራ ማስቀረት ነው።
ጆን ፎርድ
ጡረታ የወጣ ተዋናይን ሚና በመጫወት እስካሁን ስኬታማ የሆንኩ አይመስለኝም፡፡ እናም እዚያ ላይ መስራት እፈልጋለሁ፡፡
ሰን ፔን

Published in ጥበብ

“ቦሮዲኖ እና መርከቡ” የተሰኙት ግጥሞች በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብዙም የማይታወቀው የሩሲያዊው ገጣሚ የሚሃይል ሌርሞንቶቭ ሥራዎች ናቸው፡፡ ከሥራዎቹ በፊት ስለ ገጣሚው ግለ ሕይወት ባጭሩ እነሆ፡፡
ሚሃይል ዩሪቺቪች ሌርሞንቶቭ እ.ኤ.አ በ1814 ሞስኮ ውስጥ ነው የተወለደው፡፡ ከጠላቱ ጋር ተፋልሞ የተገደለውም በ1841 ዓ.ም ሲሆን ገጣሚው በዚህች ምድር ላይ የኖረው ለ27 ዓመታት ብቻ ነው።
ሩሲያ ካፈራቻቸው ታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች አንዱ የሆነው ሌርሞንቶቭ፤ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ከሴት አያቱ ጋር ሲሆነ የኖረውም ግፍና ጭካኔ በነገሰበት የሩሲያ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ ነው፡፡ ይኸውም የታህሳሳውያን ዐመፅ፣ እየተባለ የሚታወቀው ታሪካዊ ወቅት ላይ ነው፡፡ ለዚህም ነው በግጥሞቹ ውስጥ የዐመፅ የጀግንነትና የብቸኝነት ስሜት የሚያንጸባርቀው፡፡ እናም በዚያ ጭካኔ በተመላበት ወቅት ለሕዝብ አጋርነት፣ ነጻትና ደስታ ለመታገል ብርቱ ምኞት ነበረው፡፡ በተለይም በኢሚሊያ ፑጋቾቭ የተመራው የሩሲያ ገባሮች ዐመፅና እ.ኤ.አ በ1812 በሩሲያ ላይ የተፈጸመው የፈረንሳዩ መሪ የናፖሊዮን ቦናፓርት ወረራ በሕጻኑ ሌርሞንቶቭ አእምሮ ላይ የአገርና የህዝብ ፍቅር ስሜት አሳድረውበት ነበር፡፡ በዚህ መንገድ የእነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች ተጽዕኖ በሥራዎቹ ላይ ጎልቶ ለመታየት ቻለ፡፡
ሌርሞንቶቭና ትምህርት
ሌርሞንቶቭ እ.ኤ.አ በ1828 ዓ.ም በሞስኮ ዩኒቨርሲቲ ሥር በነበረው አዳሪ ት/ቤት ገባ፡፡ ይህ ት/ቤት በሩሲያ በወቅቱ ከነበሩ የትምህርት ተቋማት በጣም የተሻለና የተመረጠም ነበር፡፡ ሌርሞንቶቭ በአዳሪው ት/ቤት በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ በንቃት ይሳተፍ ነበር፡፡ በተጨማሪም ሙዚቃንና ሥዕልን ጨምሮ ለመማር ዕድሉን አግኝቷል፡፡
ሌርሞንቶቭ በአዳሪ ት/ቤቱ በርካታ መጻሕፍትን በማንበብ ዕውቀቱን አበልጽጓል፡፡ ለእርሱ ምርጥና ተወዳጅ ደራሲ የነበረውም እንደ ጓደኛው የሚያየውና የሚያውቀው አሌክሳንደር ፑሽኪን ነው፡፡ በዚያው ወቅት ሌርሞንቶቭ በጭቆናና በብዝበዛ ላይ የተመሠረተውን የገባርነት ሥርዓተ ማኅበር የሚቃወሙና በአገር ፍቅር ስሜት ላይ ያተኮሩ ግጥሞችንና ሌሎች ሥራዎቹን መጻፍ ጀመረ፡፡ በሥራዎቹም ውስጥ የአሌክሳንደር ፑሽኪን ተጽዕኖ ጎልቶ ይታይ ነበር፡፡ በጊዜው የሞስኮ አዳሪ ት/ቤት ተማሪዎች በሩሲያ ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ትኩረት በማድረግ ስለወደፊቷ ሩሲያ እጣፈንታ ይከራከሩና ይወያዩ ነበር፡፡ በመንግሥት የተከለከሉ የፑሽኪንና የታህሳሳውያንን ግጥሞች ያነብቡ ነበር፡፡ መንግሥት ደግሞ ይህን የወጣቶች የአዳሪ ት/ቤት እንዲዘጋና ተማሪዎች እንዲበተኑ አደረገ፡፡
እ.ኤ.አ በ1830 ሌርሞንቾቭ ሞስኮ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ በዚያ ወቅት (1830) በፈረንሳይ የንጉሠ ነገሥቱን የቡርቦኖቭን መንግሥት ያስወገደውና በታሪክ የፓሪስ ኮሚዩን እየተባለ የሚታወቀው አብዮት ተካሄደ፡፡ የፈረንሳይን መሳፍንትና መኳንንት የበላይነትና የፖለቲካ ሥልጣን የደመሰሰው አብዮት በከፍተኛ ደረጃ በመላ አውሮፓ ተስፋፋ፡፡ በዚያው ዓመት በበጋና በፀደይ ወቅት የሩሲያ ገበሬዎች ንቅናቄ ተካሄደ፡፡ ሌርሞንቶቭ ይህንኑ የገበሬዎች ዐመፅ ተገንዝቦ ትንቢት በሚል ርዕስ በሩሲያም አብዮት የማይቀር መሆኑን የሚያመለክት ግጥሙን ጻፈ፡፡ ገጣሚው ወግ አጣባቂ በሆነው ሥርዓት ውስጥ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት ይጠላው ስለነበር በፍጥነት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋረጠ፡፡
ሌርሞንቶቭ እ.ኤ.አ በ1832 ዓ.ም ወደ ፒተርስበርግ ከተማ በመሔድ ወታደራዊ ጦር ት/ቤት ገባ፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ የመድፈኝነት ሥልጠናውን አጠናቅቆ በመኮንኖች የጦር ክፍል ተመደበ፡፡ በወቅቱ ፒተርስበርግ ከተማ እያለ በዙሪያው የመሳፍንት ማኅበረሰብ አባላት ነበሩ። ገጣሚው ከእነዚህ ወገኖች ራሱን አግልሎ ከተናቀው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ወገነ፡፡ እ.ኤ.አ በ1835 ማስከራድ የተሰኘ ድራማ ጻፈ፡፡ የድራማው ይዘት ስለሩሲያ መሳፍንት ሁኔታ የሚያትት ሲሆን የድራማው ዋና ገጸ ባህርይ የቭጌኒ አርቤኒን ነው። አርቤኒን ገባርነትን የሚጸየፍ የወደፊቷን የሩሲያ ብሩህ ዘመን የሚናፍቅ፣ነፃ አዋቂ ወጣት የመሳፍንት ወገን ነው፡፡ ይህ ወጣት ፍቅር፣  ደግነት፣ ሰላምና ብልጽግና ያለበትን ሕይወት ይመኛል፡፡ ነገር ግን የመሳፍንቱ ማህበረሰብ አባላት እርሱን ይጠሉታል፡፡ ከዚህ ድርጊቱ የተነሣም የመሳፍንት ወገን የሆነችው ባለቤቱ ኒና ለእርሱ ታማኝ እንዳልሆነች ወሬ ይነዛል፡፡ የቭጌኒ አርቤኒንም ኒና በላዩ ላይ ማገጠች ብሎ ይገድላታል፡፡ ማስካርድ ማለትም ውሸት፣ አታላይነት፣ አጭበርባሪነት ማለት ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1837 ታላቁ ገጣሚ አሌክሳንደር ፑሽኪን ሲገደል፣ ሌርሞንቶቭ “የገጣሚው ሞት” የተሰኘ ግጥም ጽፎ ለታላቁ ገጣሚ ያለውን አክብሮትና ፍቅር ገለጸ፡፡ ግጥሙም የባላባትና የመሳፍንት ወገኖችን በእጅጉ አስደነገጠ፡፡ ከዚህም የተነሣ የተጋጋለውን የሕዝብ ቁጣ ለማብረድ እንዲቻል ንጉሠ ነገስቱ ኒኮላዎስ፤ ሌርሞንቶቭን ወደ ደቡባዊቷ የሩሲያ ግዛት ወደ ካውካሰስ ላከው። በጊዜው ሩሲያ ከቱርክ ጋር ጦርነት የጀመሩበት ጊዜ ነበር፡፡ ሎርሞንቶቭ በደቡብ የሩሲያ ግዛት በቁም እስረኝነት በመኖር ላይ እንዳለ “ዘመናዊ” (ሰብሪሜኒክ) በሚል ይታወቅና ፒተርስበርግ ከተማ ይታተም በነበረው መጽሔት ላይ ቦሮዲኖ የተሰኘ ግጥሙን አሳተመ፡፡ ቦሮዲኖ በሞስኮ አካባቢ የሚገኝ የገጠር መንደር ሲሆን በዚያ ቦታ ላይ ፈረንሳዮች በ1812 በማርሻል ኩቱዞቭ በተመራው የሩሲያ ጦር ድል ተመትተው ተበታትነው የተሸነፉበት  የጦርነት ቦታም ነው፤ቦሮዲኖ፡፡
ሌርሞንቶቭ ይህንን ሥራውን (የቦሮዲኖን ታሪካዊ ክስተት) የጻፈው በተራ የሩሲያ ቋንቋ ነው። ሌርሞንቶቭ በካውካሰስ ውስጥ ብዙ ጉብኝት አድርጓል፡፡ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ሥነ ተረት፣ ቅርስ፣ ኪነ ሕንጻ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ቦታዎችን ማየቱ፣ ማጥናቱና ማወቁ ለፈጠራ ስራዎቹ ታላቅ ግብዓት ሆኖታል፡፡
እ.ኤ.አ በ1832 መርከቡ የተሰኘ ግጥሙን ጻፈ። ሌርሞንቶቭ፤ ቀዩ የጀልባ አውታር የሚታየው ርቀትና ጥልቀት (ዕመቀ ዕመቅ) ባለው ባሕር ላይ ነው በሚል ይዘት በጻፈው ግጥሙ አማካይነት የብቸኝነትን ሕይወት አሳይቷል፡፡ በካውካሰስ ተራራ ሥር ታላቁ ጥቁር ባሕር ተዘርግቶ የሚታይ መሆኑንም ልብ ይሏል፡፡
መርከቡ
ፀዓዳ ሆኖ ታየ አውታሩ መርከቡ፣፣
በባሕር ላይ ጉዞ እያንገዋለለው ማዕበል ወዠቡ።
ምንስ ይፈልጋል ከሩቅ ሀገር ሔዶ፣
በባዕዳን መሬት ላይ ለምንስ ተገድዶ?
የመርከብ ምሰሶው ጠንካራ ቢሆንም
ፍሰሐ ተጨንቆ ደስታን አይፈልግም፣ ለማግኘት ወደፊት አይሮጥም፡፡
ከጀልባውም በታች ከውሀው ነጸብራቅ፣
ይታያል ሰማዩ አምሮ ሲብረቀረቅ፡፡
በማዕበሉ ውስጥ በበዛበት ትግል፣
ጸጥታና ሰላም ያገኙ ይመስል፣
የወርቅ ዘንግ መስለው በሚፍለቀለቁ፣
በፀሐይ ጨረሮች ወደ ጥልቁ ባሕር በተፈነጠቁ፡፡
የመርከቡንን አውታር አየሁት በሩቁ፡፡
እንግዲህ ይህ ግጥም የተገጠመው ጭንቀት፣ ውጥረትና አምባገነንነት በነገሡበትና የታህሳሳውያን ትግል በታፈነበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ከባላባት ማኅበረሰብ አብራክ የተከፈሉ ወጣቶች በሥርዓቱ ደስተኞች አልነበሩም፡፡
ትርጉም የለሽ ህይወት መኖር የሰለቻቸው ዘመናውያን ወጣቶች ስለነጻነት፣ ስለአብዮታዊ ትግልና ስለድል አጥብቀው ተመኙ። በመሆኑም በአልተደራጀ መልኩ ታህሳሳውያን በብቸኝነት የመሩትን ትግል ከዳር ለማድረስ ተነሳሱ።
እ.ኤ.አ በ1838 ሌርሞንቶቭ ከቁም እስረኝነት ተላቅቆ ወደ ፒተርስበርግ እንደተመለሰ፣ “ሚስሪ” እና “ዲሞን” የተሰኙ ሥራዎቹን አጠናክሮ ይሠራ ጀመር፡፡ “ሚስሪ” የግሪክ ቃል ሲሆን መነኩሴ ለመሆን የተዘጋጀ ሰው ማለት ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1840 የዘመናችን ሸግና የተሰኘ ልቦለድ መጽሐፍ ደረሰ፡፡ የመጽሐፉ ዋና ገጸ ባሕርይ ፒቾሪን የተባለ ወጣት መኮንን ነው፡፡ መኮንኑ ነጻነት ወዳድ፣ ዐዋቂና በካውካሰስ ወታደራዊ ት/ቤት በመማር ላይ የሚገኝ ሰው ነበር፡፡
ፍልሚያና የገጣሚው ሞት
 ሌርሞንቶቭ ወደ ግዞት በሔደበት ወቅት እግረ መንገዱን በፒተርስ በርግ ከተማ ቆይታ አድርጎ ነበር። በአጋጣሚም በዚያው ቦታ ማን አለብን ባዮች፣ ጨቋኝ ገዥዎች፣ በዕውቀቱና በነጻነት ወዳድነቱ፣ በታጋይነቱ ቀንተው ሊገድሉት ይፈልጉት ነበር፡፡ እነዚያ ጠላቶቹ ፈጽሞ ይቅርታ ሊያደርጉለት አልፈለጉም፡፡ ከዚህም የተነሳ ነጻነት ወዳዱን ሌርሞንቶቭን ለፍልሚያ ጠሩት፡፡ ከጠሩት ውስጥ እንዲገድለው ተዘጋጅቶ የነበረው የጦር መኮንን ማርቲኖቭ አንዱ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ሐምሌ 15 ቀን 1841 ከፒተርስበርግ ከተማ ሳይርቅ በሚገኝ ቦታ ላይ ገጣሚው በፍልሚያ ላይ ተገደለ፡፡ የሞቱን ዜና ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳሚዊ ኒኮላዎስና የመሳፍንትና የባላባት ወገኖች ሰምተው በደስታ ሰከሩ፡፡ ሌርሞንቶቭ ሲታገልለት የነበረው ድሀው የሩሲያ ሕዝብ ግን የደም ዕንባ አለቀሰለት፡፡
ከዚያ ዘመን ጀምሮ የገጣሚው የሌርሞንቶቭ ሥራዎች በሩሲያ ሥነ ጽሑፍ ዘንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለአሳደሩ እንደነ ቤሊንንስኪና ደብሮሉቦቭ በመሳሰሉ የሥነ ጽሑፍ ሃያሲያን ዘንድ በእጅጉ ትኩረት  ለመሳብ ችሏል፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 21 March 2015 10:31

የፍቅር ጥግ

ፍቅርንና ጉንፋንን መደበቅ አይቻልም፡፡
ጆርጅ ኸርበርት
የብቸኝነት እስረኛ ሆኖ የሚያውቅ ሰው፣ የፍቅር እስረኛ ሆንኩ ብሎ አያማርርም፡፡
ሮበርት ብራውልት
ፍቅር፤ ማብሪያ ማጥፊያውን ሌላ ሰው የሚቆጣጠረው የኤሌክትሪክ ብርድልብስ ነው፡፡
ካቲ ካርሊሌ
ህይወት የሚጀምረው ፍቅር ሲመጣ ነው፡፡
“Bill of Divorcement” ከ
ሚለው ፊልም”
ትክክለኛውን ፍቅር ከመፍጠር ይልቅ ትክክለኛውን አፍቃሪ በመፈለግ ጊዜ እናጠፋለን፡፡
ቶም ሮቢንስ
ፍቅር የህይወት ህግ ነው፡፡
ሞሃንዳስ ካራምቻንድ ጋንዲ
ፍቅርን በልብ ቅርፅ የምንስለው የነፍስን ቅርፅ ስለማናውቀው ነው፡፡
ሮበርት ብራውልት
ላንቺ ያለኝን ፍቅር ሁሉ ለመሸከም 100 ልቦች በቂ አይደሉም፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
ፍቅር ሰዎችን ይፈውሳል - ሰጪዎቹንም ተቀባዮቹንም፡፡
ካርል ሜኒንገር
ፍቅር እንደ ድንጋይ ባለበት ዝም ብሎ አይቀመጥም፤ እንደ ዳቦ መጋገር አለበት፤ ሁልጊዜ እንደገና መሰራት፣ እንደ አዲስ መፈጠር ይኖርበታል፡፡
ኡርሱላ ኬ.ሊ.ጉይን
መሸ ተብሎ የፍቅር ጨዋታ አይቀርም፡፡
ቶም ማሶን
ፍቅር የያዘው አዛውንት፣ እንደ ክረምት አበባ ነው፡፡
የፖርቹጋሎች ምሳሌያዊ አባባል
ፍቅር የስሜቶች ቅኔ ነው፡፡
ኦኖር ዲ ባልዛክ
ፍቅር ሁለቱም ተጫውተው ሁለቱም የሚያሸንፉበት ጨዋታ ነው፡፡
ኢቫ ጋቦር

Published in ጥበብ
Saturday, 21 March 2015 10:29

ከበደች ተክለአብ አርአያ

ሰዓሊ፣ ቀራጺ፣ ገጣሚ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህር
  የስነጥበብ ትምህርት መማር የጀመርኩት በአዲስ አበባ የስነጥበብ ትምህርት ቤት በ17 ዓመቴ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ በስነጥበብ ሙያ እተዳደራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ስነጥበብን የመስራት ፍላጎት ብቻ ነው የነበረኝ፡፡ ህይወት ግን መንገዴን ወደ ስነጥበብ አቅጣጫ መራችው፡፡ በደርግ የአገዛዝ ዘመን በተካሄደው የተማሪዎች ንቅናቄ ተሳትፎ በማድረጌ መታደን ስጀምር፣ በጅቡቲ በኩል ለማምለጥ ሞከርኩ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን በወቅቱ ሶማሊያና ኢትዮጵያ በድንበር ግጭት ውስጥ ስለነበሩ፣ ድንበር ላይ የነበሩ የሶማሊያ ወታደሮች በቁጥጥር ውስጥ አዋሉኝ፡፡ ቀጣዮቹን አስር አመታት ያሳለፍኩት በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ስራ ካምፖች ውስጥ ነበር፡፡ ህይወት ግን ለሁሉም ነገር ምክንያት ነበራት፡፡ “በገሃዱ አለም የምናስተናግዳቸው ሽንፈቶቻችን፣ በስነጥበቡ አለም ድሎቻችን ይሆናሉ፡፡ በስነ ውበት አይን ሲታይ፤ ችግሮቻችንን፣ ስቃዮቻችንንና ሽንፈቶቻችንን በመውደድና በእነሱ ከመማረር ይልቅ ወደ ስነጥበብ ስራነት በመቀየር፤ የኋላ ኋላ በቁጥጥራችን ውስጥ እናደርጋቸዋለን” በማለት ጽፋለች ሜልቪን ራደር። በእስር ቤት ያሳለፍኳቸው አመታት፣ ከተቀረው አለም የሰው ልጅ ጋር ትስስር ለመፍጠሬ ሰበብ ሆነውኛል፡፡ ለስነጥበብ ስራዎቼ የመነቃቃት ምንጭ የሆኑኝም እነዚያ የግዞት አመታት ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ መርካቶ የሚባለው ሰፈር ውስጥ በ1950 ዓ.ም ነው የተወለድኩት፡፡ መጠነኛ ገቢ ያላቸው ወላጆቼ ካፈሯቸው አራት ልጆች፣ እኔ የመጨረሻዋ ነኝ፡፡ ዛሬም ድረስ የሚከተለኝን ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረችብኝ አሁን በህይወት የሌለችው እናቴ ናት፡፡ እናቴ መንፈሳዊውን አለም ከምድራዊው አለም ጋር በሚገርም ሁኔታ አጣጥማ ህይወቷን ስትመራ የኖረች፣ ፍጹም ሃይማኖተኛ፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነበረች፡፡ መደበኛ ትምህርት ባትከታተልም እጅግ ብሩህ አእምሮ ያላትና ለስነጽሁፍ ፍቅር የነበራት ሴት ነበረች። የማክሲም ጎርኪን መጽሃፍት አነብላት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከጎርኪ ስራዎች፣ ‘እናት’ ለሚለው ረጅም ልቦለድ የተለየ አድናቆት ነበራት፡፡ አማርኛ ማንበብና መጻፍ የቻለችው በራሷ ጥረት ነው፡፡ ለስነግጥም፣ በተለይ ደግሞ ለቅኔ እንዲሁም ለቲያትር የተለየ ፍቅር ነበራት፡፡ የስነጥበብ ስሜትም ነበራት። የራሷን የጥልፍ ዲዛይኖች ትሰራ ነበር፡፡ ለፍትህ መከበር ጠንካራ አመለካከት ያላት እናቴ፣ ከቁሳዊ ስኬቶች ይልቅ ለእሴቶች ራሳቸውን ከሚያስገዙ ጥቂት ሰዎች አንዷ ነበረች፡፡ በትምህርት አጥብቃ ታምናለች፡፡ አባቴ ወደ መቀሌ ከተማ ሄዶ መድሃኒት ቤት ሲከፍትና ፊቱን ወደ ንግድ ሲያዞር፣ እሷ ግን እኛን ልጆቿን ለማስተማር አዲስ አበባ መቅረትን ነው የመረጠችው፡፡ ከትምህርት ቤት ስንመለስ  ውሏችንንና የተማርነውን  ትጠይቀናለች፡፡ የቤት ስራችንን በአግባቡ እንድንሰራም ታበረታታናለች፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህራን  መጽሃፍትን ሲያነቡልን በጽሞና አዳምጣቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይሄን የማደርገው ወደ ቤቴ ስመለስ ታሪኩን በአግባቡ ለእናቴ ለመተረክ ስል ነበር፡፡ እናቴ ሁሌም ከጎኔ ነበረች፡፡ በተደጋጋሚ ባጋጠሙኝ ፈታኝ የመከራ ጊዜያት ሁሉ በጽናት እንድቆም ትደግፈኝ ነበር፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ስነጽሁፍ የመማር ሃሳብ  ነበረኝ፡፡ ንባብ ስወድ ለጉድ ነው፡፡ ግጥም ነፍሴ ነው፡፡ ቅኔ የመማር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እየሄድኩ ግዕዝ መማር የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ በተቀሰቀሰው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ በየጉራንጉሩ ግጥሞችን እየጻፉ መበተን ትልቅ የትግል ስልት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ግጥሞችን መጻፍ የጀመርኩት፡፡ እርግጥ የስዕል ስሜትም ነበረኝ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሆኜ፣ የሳይንስ ትምህርት ስዕሎችን መሳል እወድ ነበር፡፡ በስተመጨረሻም ስዕልና ቀለም ቅብ ይወዱ የነበሩት ወንድሜና አንድ ጓደኛዬ  ባሳደሩብኝ ተጽዕኖ፣ አስራ አንደኛ ክፍልን ተምሬ እንደጨረስኩ ስነጥበብ ለማጥናት ወስኜ፣ በ1968 ዓ.ም በአዲስ አበባ የስነጥበብ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ለአንድ አመት ከመንፈቅም ትምህርቴን ተከታተልኩ፡፡
በቀበሌና በወጣት ሊግ አማካይነት በተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳትፎ ማድረጌን ቀጠልኩበት፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ወታደራዊው መንግስት፤ የቀይ ሽብር ዘመቻን አውጆ ተማሪዎችን ከያሉበት እያደነ ማሰርና በጅምላ መጨፍጨፍ ሲጀምር፣ እኔም ለዚህ ክፉ ዕጣ ከታጩት ታዳኝ ተማሪዎች አንዷ መሆኔን አወቅሁት፡፡ ከተጋረጠብኝ አደጋ ማምለጥ ነበረብኝ፡፡ ለአንድ አመት ከመንፈቅ ያህል ከሌሎች አምስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ተደብቀን ቆየን፡፡ በስተመጨረሻም ድንበር አቋርጠን ጅቡቲ ለመግባትና ጥገኝነት ለመጠየቅ በማሰብ፣ በ1971 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወጣን፡፡ በድብቅ ድንበሩን ሊያሻግሩን ፈቃደኛ የሆኑ ነጋዴዎች ብናገኝም፣ ሙከራችን ግን እጅግ አደገኛ ነበር፡፡ አቋርጠነው ልናልፍ ባሰብነው ድንበር ላይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ገጥመው ነበር፡፡ ይህ መሆኑን ሳናውቅ ነው፣ በእግራችን ጉዞ የጀመርነውና የሶማሌ መደበኛ ጦርና  የሶማሊያ ነጻ አውጪ ግንባር ወታደሮች ሰፍረውበት ወደነበረው የጦር ካምፕ ሰተት ብለን የገባነው። በቁጥጥር ስር ውለን ወደ ሶማሊያ ተወስደን ታሰርን። በሁለቱ አገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ከሶስት አመታት ጦርነት በኋላ ቢጠናቀቅም፣ እኛ ግን ቀጣዮቹን አስር አመታት ያሳለፍናቸው በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ስራ ካምፖች ውስጥ ነው፡፡ በስተመጨረሻም በኢጋድ ስብሰባ ላይ በተደረገ ስምምነትና በአለማቀፉ የቀይመስቀል ድርጅት አግባቢነት ይመስለኛል፣ ሁለቱ አገራት የጦር እስረኞችን ለመልቀቅ ፈቃደኞች ሆኑ፡፡ እኛም በ1981 ዓ.ም ከእስር ተፈታን፡፡
እነዚያ በእስር ያሳለፍናቸው አመታት እጅግ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ከእስር ቤቱ ቅጽር ውጪ ካለው አለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረንም። ከጉሮሮ የማይወርድ ምግብ እየበላን፣ ንጽህና በጎደለው ማጎሪያ ውስጥ አስከፊ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ውለን ማደር ነበረብን፡፡ ወባና በደም ኢንፌክሽን የሚፈጠረው ቺስቶሶሚያሲስ የተባለ በሽታ፣ ዘወትር ከእስር ቤቱ የማይጠፉ የተለመዱ የእስረኞች የስቃይ ምንጮች ነበሩ፡፡ ልንፈታ አንድ አመት ገደማ ሲቀረን፣ የኮሌራ ወረርሽኝ ሳይቀር ተከስቶ ነበር፡፡ እስር ቤት ውስጥ፣ ፍጹም ስለ ራሳቸው ግድ የሌላቸው አልያም ፍጹም አደገኛና ራስ ወዳድ ሰዎችን ልታገኚ ትችያለሽ፡፡ እኛ ጋ ሁለቱም አይነት ሰዎች ነበሩ፡፡ ፈጣሪ ከዚያ መከራ ያተረፈኝ ለእናቴ ብሎ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እሷ ለኔ ከፈጣሪ የተሰጠችኝ ትልቅ ስጦታ ነበረች፡፡
 እንደ እስረኛ እርስ በርስ እንረዳዳ ነበር - በቁሳቁስ ሳይሆን መከራን አብሮ በመጋፈጥ። የጽሁፍ መሳሪያዎችን  ባገኘሁበት አጋጣሚ ሁሉ፣ በርካታ ግጥሞችን ጽፌያለሁ፡፡ የመድሃኒት ፓኮዎችንና የዱቄት ወተት ክርታሶችን እንደ ወረቀት እየተጠቀምን ነበር የምንጽፈው፡፡ እርግጥ በአማርኛ መጻፍ ክልክል ስለነበር፣ የጻፍኳቸውን ግጥሞች በየስርቻው እደብቅ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ግጥሞቼ በአይጥና በድመት ተበልተዋል፣ በርካቶችም ጠፍተዋል፡፡ መጻፌ ከአእምሮ መቃወስ አድኖኛል። ቀስ በቀስ ትምህርት ቤት አቋቁመን ለእስረኞች ፊደላትን ማስቆጠርና ሌሎች ትምህርቶችን ማስተማር ጀመርን፡፡ ሳይንስ እና እንግሊዝኛን የመሳሰሉ ትምህርቶችን አስተምር ነበር፡፡ ትልቁ አስተዋጽኦዬ አማርኛ ማስተማር ሲሆን የተለያዩ ታሪኮችና ግጥሞችን እየጻፍኩ ለማስተማሪያነት እጠቀምባቸው ነበር፡፡ እኛ ከእስር ስንፈታ ማንበብና መጻፍ የማይችል እስረኛ አልነበረም። ትምህርቱም እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል አድጎ ነበር፡፡ መጽሃፍትን የምናገኘው አልፎ አልፎ ነው። በተለየ ሁኔታ የማስታውሳቸው፣ የፕሪሞ ሌቪን መጽሃፍትና የአሌክስ ሄሊን ‘ሩትስ’ የተሰኘ መጽሃፍ ነው፡፡ በሄሊ መጽሃፍ ውስጥ የተሳሉት የመስክ ሰራተኞች ህይወት፣ ከእኛ ህይወት ጋር በሚገርም ሁኔታ መመሳሰሉ ቀልቤን ማርኮት ነበር፡፡ ራሳችንን ዋጋ እንዳለው ሰብአዊ ፍጡር እንድናስብ ያገዙን  እነዚህ ነገሮች ናቸው፡፡
እንደተፈታሁ ወዲህ ወዲያ ሳልል በቀጥታ የመጣሁት ወደ አዲስ አበባ ነበር፡፡ ምክንያቱም ወንድሜ እኔን ፍለጋ አዲስ አበባ መምጣቱን ሰምቻለሁ፡፡ ወንድሜ ያንን ማድረጉ ለእኔም ሆነ ለእሱ አደገኛ ነበር፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ኢትዮጵያን ለቅቄ፣ መላው ቤተሰቦቼ ወደሚኖሩባት አሜሪካ አቀናሁ፡፡ ከረዥም ጊዜያት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከእናቴ፣ ከወንድሜ፣ ከእህቴና ከቀሩት ቤተሰቦቼ ጋር ለመቀላቀል ቻልኩ። ለዓመታት ያቋረጥኩትን የስነጥበብ ትምህርት በመቀጠልም፣ በዋሽንግተን ዲሲው  ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ በስነጥበብ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዬን አገኘሁ፡፡ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ስከታተል ግሩም  መምህራን  ገጥመውኛል፡፡ ሁለት ድንቅ መካሪ ዘካሪም  አግኝቻለሁ፡፡ የስነጥበብ መምህሬ እስክንድር ቦጎሲያንና የፊልም መምህሬ አብይ ፎርድን፡፡ ከእስክንድር ጋር በመሆን ‘ኔክሰስ’ የተሰኘ የሥነጥበብ ስራ ዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የመስራት እድል አግኝቻለሁ፡፡
በስዕሎቼ ስሜቶቼን፣ ትዝታዎቼን እንዲሁም ጊዜና ቦታ ከሚገድባቸው ግላዊ ገጠመኞቼ፣ ዘመን እስከማይሽራቸው አለማቀፍ ጉዳዮች የተዘረጋውን ምናቤን መግለጽ ጀመርኩ፡፡ ራሴን በግላዊ ገጠመኞቼና ልምዶቼ ላይ ብቻ አልገደብኩም። ምናቤን ሰፋ በማድረግ ጦርነት፣ ስቃይና በስተመጨረሻም ፈውስን ወደመሳሰሉ አለማቀፍ ጉዳዮች ገባሁ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ፣ በቀላሉ የሚለዩ የእይታ ተረኮችን በመጠቀም የግል ልምዶቼን በአለም ዙሪያ ከሚታዩ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ጋር እያስተሳሰርኩ፣ ኤክስፕሬሽኒስት በተባለው የአሳሳል ዘዬ ነበር ስዕሎቼን የምሰራው። በመቀጠልም ከዚህ ቀደም እንደማደርገው ሁሉ ትኩረቴን በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በማድረግ ከቀድሞዎቹ በበለጠ ምስል አልባ የሆኑ ወይም አብስትራክት ስዕሎችን መስራት ጀመርኩ፡፡ ከዚያም ቴክስቸር፣ ቀለምና ቅርጽን በመሳሰሉ የእይታ  መሰረታዊ ነገሮች በመጠቀም፣ ስሜትን የሚያጭሩ ሙሉ ለሙሉ ምስል አልባ ወይም አብስትራክት ስዕሎችን መሳል ቀጠልኩ፡፡ አሁን ብርን የመሳሰሉ ባህላዊ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በመገጣጠም እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ብር በውስጡ ብርሃን ስለሚያሳልፍ እወደዋለሁ፡፡ ከሌሎች ቁሳቁሶች ጋር በመሸመን የተለያዩ ተደራራቢ ትርጉም ያላቸው መልዕክቶችን ማስተላለፍ መቻሌ ያስደስተኛል፡፡ ስዕሎችንና ቅርጻቅርጾችን ከስነግጥም፣ ሙዚቃና ስነጽሁፍ ጋር እያዋሃድኩ የራሴን ህብር እፈጥራለሁ፡፡ አንደኛው ጥበብ በሌላኛው እንዲሁም በእኔ ላይ መነሳሳትና ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡
ከሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅኩበት ጊዜ ጀምሮ፣ በስቱዲዮ ስራዬን እየሰራሁ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስነጥበብ ትምህርት አስተምር ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጆርጂያ በሚገኘው ሳቫና የስነጥበብና የዲዛይን ኮሌጅ እያስተማርኩ እገኛለሁ፡፡ መምህር መሆኔን እወደዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ራሴን ሙያው በየጊዜው ከሚደርስበት  ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለማድረስ ስል፣ በስፋት እንዳነብና ጥናት እንዳደርግ ያስገድደኛል፡፡ ሌላው ሙያውን እንድወደው የሚያደርገኝ ነገር ደግሞ፣ ከዚህ በፊት ልምዱ ባልነበረኝ የስነጥበብ ጉዞዎች ላይ በተደጋጋሚ እንድሳተፍ ዕድል የፈጠረልኝ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም በሌሎች የአፍሪካ አገራት ባስተምር ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም በሙያዬ  የማበረክተው አስተዋጽኦ በእነዚህ አገራት የተሻለ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ ቀን የሙሉ ጊዜ የስቱዲዮ ሰዓሊ የምሆንበትና በጽሁፍ ስራ ላይ ብዙ ጊዜዬን ማሳለፍ የምችልበት ዕድል ይፈጠርልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስነጥበብ ለኔ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ነገር ነው። ስነጥበብን የምኖርለት ሙያዬ ለማድረግ ችያለሁ ብዬ የማስበው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንድም ስለ ቁሳዊ ስኬት ተጨንቄ አላውቅም፡፡ ሁለትም ሙያው የሚጠይቀውን ዲስፕሊን አክብሬና ሙሉ ትኩረቴን በእሱ ላይ አድርጌ ነው የኖርኩት፡፡
የዛሬ ዘመን ወጣት ሴቶች ትኩረት ሊሰጧቸው ይገባሉ የምላቸው ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ነገር አደጋዎችን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። ፈቃደኛ ካልሆኑ ምንም ነገር ሊያሳኩ አይችሉም። አደጋን መጋፈጥ በህብረተሰቡ ዘንድ ሰርጸው የኖሩና ቅቡል የሆኑ አመለካከቶችን መገዳደር ሊሆን ይችላል፡፡
ሴቶች ይህን ማድረጋቸው ህልማቸውን እውን ለማድረግ ያግዛቸዋል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ አደጋን መጋፈጥንና ከባህል  ልንማራቸው የምንችላቸውን ነገሮች ማክበራችንን በተመጣጠነ ሁኔታ ማስኬድ ይኖርብናል፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ወጣት ሴቶች እውቀትን መሻት ብቻ ሳይሆን እውቀትን ፍለጋ ከተጉ፣ ግሩም የሚባሉ ነገሮችን ለማሳካት እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡
(ሰዓሊና ገጣሚ ከበደች ተክለአብ የዛሬ 15 ዓመት አዲስ አድማስ መታተም ስትጀምር  የጋዜጣው እንግዶች ሆነው ከቀረቡት የጥበብ ባለሙያዎች መካከል ቀዳሚዋ ነበረች፡፡ ከላይ የቀረበውን ግለ ታሪክ የወሰድነው ባለፈው ጥቅምት ወር ለንባብ ከበቃውና የስኬታማ ኢትዮጵያውያንን ሴቶች ታሪኮች ከሚያስነብበው ተምሳሌት የተሰኘ መጽሐፍ ነው፡፡)

Published in ጥበብ
Saturday, 21 March 2015 10:28

የሰከረ እውነታ---

“የማን እውቀት የእግዜርን ስም ገለፀ?”
   ፎቅ በሚባሉ የጠረጴዛ እግሮች ስር መሽከርከር… ያለ ገደብ በሚሰፋ ስጋ ውስጥ እንደ አሲድ የሚበላ ነፍስን መሸከም… እራትን መብላት፣ መብራትም ማብራት ከመሰረታዊው ጨለማ ላያስጥል… ምክኒያት እና ውጤት ትርጉም የሚሰጥ ትስስር ላይኖራቸው… የሴራው ስር ላይጨበጥ... ግንድም ቅርንጫፍም ላያበቅል፣ የፈራ ቢመለስ ላይተርፍ፣ የደፈረ ቢገፋ ላያተርፍ … መፅሐፍት ቢነበቡ ዘላቂ ሙላት ላይሆኑ… መምሰል ከመሆን ላይነጠል… መልካም መሆንም ክፋትን መመሰል እንዲቻል ከማገዝ ላይዘል… የንፅፅር ብዥታ ግልፅነት ላይወጣው … ብክነት፡፡
ከራስ ህይወት ትርጉም አልቦነት … አንዳች የሚለወጡትን የሚከተሉት… ከወረዱት ጭራ ሆኖ የባሰ መውረድ … የመውረድ መዋረድ አዘቅት መጨረሻው ወለል መጥፋት፡፡ መውደቅ፣ መውደቅ… በቀደሙት አወዳደቅ መቅናት … የአወዳደቅ ቅርፅ እንደ ዘመን አሻራ ሲወደስ … ያልሆነውን ለመሆን… ሊሆን ይችል የነበረውን ድምጥማጡን ማጥፋት፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ የሚያድግ ነፍስ …. ስጋ ሊሸከመው የማይችል … ተቅሞ የማያልቅ ህልም … ተሩጦ የማያልቅ ሽሽት… “ሊነጋ ሲል ይጨልማል” በሚል ስብከት፣ ንጋት ከዚህ በኋላ እንደማይገኝ ቁርጡን፣ እቅጩን ማዘናጋት፡፡
የክፉዎች ክፋት… “የመልካም ዝምታ”… የፍርድ መዘግየት፡፡ የፍርድ ቀን መድረሱን የሚሰብኩ፣ ምን ያህል የትውልድ ቅጥልጥል እያደረሰ ወዳለው ለመድረስ እንደምንርቅ፣ በምናውቀው ቋንቋ ለውጠው የማይነግሩን፡፡ ማስጠንቀቅ ብቻ … የጥንቃቄ ውጤት … በክፋት ማካፈል…ተስፋን አያበራም…ያስቆርጣል እንጂ፡፡
ይህ ሁሉ ግን የሰው ጦርነት አይደለም። የተኮሰውም የገደለውም ሰው አይደለም፡፡ ተጠያቂው ብቻ ግን ሰው ነው … ዘላለማዊ ጎዶሎ እና ዘላለማዊ ሙሉ በሰውነት ላይ የሚያደርጉት ጦርነት የሰው ጥፋት ባይሆንም..ተጠያቂው ግን ሰው ብቻ ነው፡፡
የህይወት መከራ በህልም ማደንዘዣ … ተስፋ በተቆራረጠ ትንፋሽ የሚገፋው--- የሚገፋው የማይነቃነቅ ተራራ፣ እድሜ ልክ ስቃይ በዘላለም ጨለማ ተመስሎ፣ ብርሐን በመርፌ ቀዳዳ ተጮልቆ ሲታይ ትርጉም ያለው መስሎ… ርቆ ተሰቅሎ … ትርጉም በትርጉም ሲለወጥ … ፎቅ የያዕቆብን መሰላል ሲመስል … ያዕቆብ በመሰላሉ ስር ሲሽሎከሎክ … ትርጉም ትርጉምን ሲገድል … የገደለ ስለማዳኑ ሲመሰክር …
በዚህ ውስጥ ነፍስ ቦታዋ የት ነው፤ የት ሆና ነው አድጌያለሁ የምትለው? አድጋ ማን ሊሸከማት…ተጠቅልሎ የተኛ መንፈስ ፈሪ ወይንስ ደፋር የሚባለው?
በትንንሽ ነገሮች መጠመድ… የሰማይ ቀለሙ ላይቀየር እይታን ለመቀየር መትጋት፣ የማይቀየረውን ውሸት ሳንሰለች እውነትን ለመቀየር መትጋት…ትጋቱን እድገት ብሎ መጥራት፡፡
የጊዜ ትርጉም በኔ ነፍስ እውቀት ላይገለፅ፣ በቁጥር ቃልን ለመሰንጠቅ፣ ቃልንም በቁጥር… የሰው ማንነት ጥላ ሆኖ ሳለ፣ መሬት የወደቀውን ጥላ ብሎ ጥላሸት መቀባት፡፡ አውሮፓ ግራ በገባው ዘመን የአውሮፓን የድፍረት ዘመን ፍልስፍና አንገትን ቀና ለማድረግ ሲባል ማጥናት…በጠረጴዛ ስር፣ በወንበር እግር ዙሪያ መሽሎክሎክ… ሮጦ የማያመልጥ ነገርን አድኖ ለመብላት የሚደረግ ሙከራ መክሸፍ…ሚዳቋን በእንስሳት መጠበቂያ የሰው ስምምነት መንከባከብ…ምድሪቱን ግን አድኖ መብላት… ብዙ ጊዜ ተበልታ አላልቅ ካለች ደግሞ እንደ ፊኛ ነፍቶ ማፈንዳት…፡፡
ክፋትን ለመረዳት ነብስ አቅም ስታጣ፣ ለማስረዳት ደጋግሞ ማስተማር የነበረበት የመልካሙ ሰማይ አስፈሪ ዝምታ፡፡ አንዴ ሲጀመር --- አንዴ ሲጨረስ ካልሆነ እጁን ለፍርድ የማያስገባው ብርሐን፤ የሰው ልጅ በጨለማ ክፋት ሲቦካ እንኳን ቃሉን አያጥፍም፣ ጣልቃ አይገባም… ጨለማ የሚቀዳድደውን የሰው ውድቀት አልፎ አልፎ በብርሐን ቅዳጅ ዋና ዋናው ስፍራ ላይ ለመጣፍ ሲል እንኳን ቃሉን አያጥፍም፡፡
በጠረጴዛ እግር ስር እና በወንበር እግር ስር መሽሎክሎክ…ማንም ብቁ ሆኖ ላልተገባለት የሰው ልጅ ሀቀኛ የደረሰ ላይኖር… ባልተቀመጠበት ክብር ላይ ወጣሁ ከማለት አለማፈር፤ አልወርድም ብሎ መፈከር፡፡
በሚያቆለቁል ሰውነት ውስጥ ነፋስ መቀመጫዋ የት ነው? የሚሸከማት አቅም በጊዜ ተሸራርፎ አልቋል፡፡ እድሜ ከዘጠኝ መቶ ዘጠኝ ቦታ ተካፍሎ ቀሪ በስተኋላ የለውም፡፡
እውቀት ማንን ወደ የት አደረሰ?...እውቀት ሰውን ወደ ነፍሱ መች መራ? የነፍስን ሸክም በስጋ ላይ መች አቀለለ፡፡ አረቄን ከስካር ነፃ መች አደረገ…በሚለያዩ ነገሮች መሀል ክፋትን እንጂ መስማማትን መች አጥብቦ አቀራረበ? አንገት እና እራስን የስራ ድርሻ ለማለዋወጥ ከመትጋት የበለጠ መች መፍትሔ አስተዋወቀ? የማን እውቀት የእግዜርን ስም ገለፀ? የማን እውቀት ተቃራኒን ከመደመር ውጭ ቀንሶ አስማማው?
እውቀት ፍርሐትን በፍቅር ይተካል አሉኝ… እራት የምሽት ረሀብን እንደሚያስወግደው… መብራት ፀሐይን ከኮርኒስ ስር ተክቻለሁ እንደሚለው---ዘላቂውን ጨለማ የሚያጠፋ ዘላቂ ፀሐይ የቱ ነው? ዘላቂ ፀሐይን የሚያጠፋው የብርሃን ምንጭ የሚሆን ያለመነሻ የሚነሳ፣ ያለማጠናቀቂያ የሚደርስ የእውቀት ንጥረ ነገር ያለው ማነው? ሙሉ የሆነ እውቀት የቱ ነው? የማይሻግት እምነት ያለው ማነው? እንደ ወጣት አፍላ ሆኖ፣ ብርቱ ደንቆሮ ወይንም እንደ አዛውንት የበሰለ ደካማ ሆኖ፣ አንድ ጐኑ ያልተሰናከለ፣ የተቃራኒ ድምር ያልሆነ እውቀት የቱ ነው?     
የቱስ ጋ ነው እውነት…ከታች ወደ ላይ እንደ ሀረግ በጠረጴዛው (ፎቁ) እግር እና በወንበሩ  ላይ ተጠምጥሞ የማያድግ… ወደ ላይ ተጠምጥሞ ያደገበት ቋሚ መቼም የማይከዳው--- ወደ ላይ እንዳደገው…ወደ ታችም ሃሳብ በተለዋወጠ ቁጥር የማይሞት እውነት…የማይለዋወጥ ክፋት ከሚለዋወጠው ቋሚ እና በቋሚው ላይ ደፋር እምነቱን እውነት ብሎ የሚጠራው በስተቀር የማይለዋወጥ ብርሃን በሰው ስጋ ከወዴት አለ?
የማያድግ ስጋ ላይ ለማደግ የሚጠመጠም ነብስ ሸክሙ ይከብዳል፡፡ እንደ አሲድ ነፍስ እና ስጋን አንድ ላይ ይበላል፡፡ የሰከረ እውነታ የህልውናን ጭንቅ ያከራል፡፡ ነፍስስ ይኼን ያህል ስጋ በተቃርኖ መሸከሙ በመስኮት ተቀምጦ በስጋ አይን በጠባብ መስኮት ውጭ ውጭ እያዩ ከመተከዝ ውጭ ምን መፍትሔ ያመጣል?
እየወደቁ መጮህ ነው ፀሎት? መውደቁ ላይቀር ፀሎት ስቃይን ከማጭበርበር ውጭ ምን ትርጉም አለው? የመጨረሻው ዘመን ላይ ነን ተብሎ የለ----ስቃይ እየባሰ እንጂ እየቀነሰ አይሄድም፤ ብለውናል፡፡ ስለዚህ ፀሎት ምልጃ ሳይሆን ምስጋና ነው መሆን ያለበት፡፡ ወደ መጨረሻችን ለመወለድ የምናደርገው ምጥ ስሙ “ምስጋና” ነው፡፡ የልጅ ልጆቻችንን እኛ ወልደን ከእኛ በላይ ስለሚሰቃዩ እናመስግን…በመሰቃየታቸው መጨረሻውን ከመጀመሪያው የሚያገናኙ እና የተጀመረው እንዲጠናቀቅ መስዋዕት የሚሆኑ ናቸው፡፡ በፈጣሪ አምናለሁ። በእግዜር አምናለሁ፡፡ እግዜርን እፈራለሁ፡፡ የሚያምን የሚፈራ የዝምታው ህግ የሚጠይቅበትን መክፈል ይኖርበታል፡፡ ከጠረጴዛው እግሮች በላይ ከጠረጴዛውና ከህይወት ሁሉ በላይ ስላለው እውነት ሲል …ሁሉንም ጨለማ ክፋቱ በስጋና በነፍሱ ላይ እየተቀያየረ የሚያከናውነውን መሸከም መቻል አለበት፡፡ ለማቅለል የሚወሰዱ አማራጮች ሁሉ መጨረሻውን ከመሆን አያግዱትም… መጀመሪያውንም አይለውጡትም፡፡ በአካሌ ግርግዳ ወጥታ ለማምለጥ የምትፍጨረጨረውን ነፍሴን ለማረጋጋት፣ የእግዜርን ንድፍ በአመፃው ውስጥ እንድትከተል ለማስገደድ ከላይ የፃፍኩትን ፃፍኩ። ለነፍስም የሚሆን መብራት፣ መልካሙ ዝምታ ከመጠን የለሽ ትእግስቱ ቀንሶ ይስጠኝ፡፡ አሜን፡፡

Published in ጥበብ

በዚህ ዓመት በሦስት ፕሮግራሞች ለነዋሪዎች ከሚተላለፉት 75ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በአቧዶ፣ በባሻወልዴ ችሎት፣ በልደታ፣ … ሳይቶች ግንባታቸው የተጠናቀቁ ከ35ሺህ በላይ ቤቶች ዕጣ ነገ እንደሚወጣ ተገለፀ፡፡               
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር፣ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት አስተዳደርና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የቤቶች ማስተላለፍ ቅድመ ዝግጅት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ በሳምንቱ አጋማሽ በካቢኔው ጽ/ቤት በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በዕጣ አወጣጡ ነባርና አዲስ ተመዝጋቢዎች እንደሚካተቱ አስታውቀዋል፡፡
በ2005 ዕጣ ከወጣ በኋላ  በተደረገው ማጣራት ከ317ሺህ ወደ 135ሺህ የወረዱት ነባር ተመዝጋቢዎች ቅድሚያ የማግኘት መብት አላቸው ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ፤ ከ10/90 እና 20/80 ዕጣ ከሚወጣላቸው ቤቶች ውስጥ ለሴቶች 30 በመቶ፣ ለመንግሥት ሰራተኞች 20 በመቶ ቅድሚያ ከተሰጠ በኋላ በቀሪው ሁሉም ተመዝጋቢዎች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል፡፡
አቶ መስፍን ከሰኔ 2005 እስከ የካቲት 2007 ባሉት 16 ወራት ውስጥ የቆጠቡ ሰዎች በመጀመሪያው ዙር በሚተላለፉት 35ሺህ ቤቶች ዕጣ ላይ ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡ በ2005 የወጣው መመሪያ ለ6 ወር ያልቆጠበ ሰው ይሰረዛል ቢልም፣ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ላይመቻቸው ስለሚችልና ዕጣው የሚወጣው በመጋቢት ስለሆነ ከተማ አስተዳደሩ ከባንክ ጋር በመመካከር እስከ ፌብሩዋሪ 28 ያጠራቀሙ ሰዎች በዕጣው እንዲሳተፉ መደረጉን፣ ከዚያ ወዲህ ቤት አገኛለሁ በሚል ተስፋ እየቆጠቡ ያሉ ሰዎች በ11ኛውና በ12ኛ ዙር እንደሚሳተፉ አስረድተዋል፡፡
ለልማት ተነሺዎች የሚሰጡትን 6ሺህ ቤቶች ጨምሮ በዚህ ዙር ለነዋሪዎች የሚተላለፉት ቤቶች ቁጥር 41 ሺህ እንደሆነ የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፤ እስካሁን ድረስ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ቤት ስላልተላለፈ፣ በነባር 20/80 ስቱዲዮ የተመዘገቡ ሰዎች በሙሉ በዚህ ዙር ያገኛሉ። ለ10/90 ቤቶች የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር 22 ሺህ ሲሆን እየተገነቡ ያሉት 10/90 ቤቶች ከተመዝጋቢው ቁጥር በላይ ስለሆኑ ከ135ሺህ ነባር ተመዝጋቢዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ በዚህ ዓመት የቤት ባለቤት ይሆናሉ ብለዋል፡
ባለፉት ዙሮች ለነዋሪዎች ይተላለፉ የነበሩት ቤቶች ግንባታቸው 20 በመቶ የተጠናቀቀ ስለነበረ ለማስረከብ ረዥም ጊዜ ይወስድ ነበር ያሉት አቶ መስፍን አሁን ግን መንግሥት 100 ፐርሰንት የተጠናቀቁ ብቻ ሳይሆን መሰረተ ልማት (መብራት፣ ውሃ፣ መንገድ…) ተሟልቶላቸው ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ በወሰነው መሰረት፣ የቤቶቹ ግንባታ የተጠናቀቀ ስለሆነ ዕጣ ከወጣ በኋላ ማጣሪያ ተደርጎ ርክክቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ መሰረተ ልማቱ ይሟላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዕጣ የወጣለት ሰው በባንክ ያጠራቀመው የአጠቃላዩን ቤት ግንባታ ወጪ 20 በመቶ ካልሆነ እንዲያሟላ ይደረጋል እንጂ አይሰረዝም ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ 20 በመቶ ማጠራቀም ያልቻለም ዛሬ ባያገኝ ነገ ሊያገኝ ስለሚችል የፕሮግራሙ አካል እንደሆነ ይቆያል፡፡ ነገር ግን በራሳቸው ፍላጎት እንዲሰረዙና ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው የጠየቁ ሰዎች መብታቸው ስለሆነ ተሰርዘው የቆጠቡትን ከባንክ መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለአክሲዮኖች ሲመዘግብ ከ24 – 3 ወራት ቤት ሰርቼ አስረክባለሁ በማለት ነበር፡፡ ነገር ግን ከአቅም በላይ በሆኑ ተጨባጭ ችግሮች ቃሉን ማክበር እንዳልቻለ ይገልጻል - ሀበሻ ኮንስትራክሽንና ማቴሪያል ልማት (ሀኮማል)፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያት ባለአክሲዮኖቼን ጠርቼ ችግሮቹን በማስረዳት ተወያይተናል ብሏል፡፡
ያለፈው ሁለት ዓመት ለቤት ገዢዎችና አልሚዎች ጥሩ ጊዜ አልነበረም፡፡ ቤቶችን በገቡት ቃል ጨርሶ ያለማስረከብና የአንዳንድ አልሚዎች ከአገር መውጣት፣ ህብረተሰቡን በከፍተኛ ስጋት ሲያምሰው ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ ጭንቀትና ስጋት አልፎ ሀኮማል በመራ ሎቄ ሳይት እያስገነባ ካለው 10 ብሎኮች አራቱን በቅርቡ ለባለቤቶች ለማስረከብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ “መሪ ሎቄ እየሰራን ካሉት 10 ጂ + 4 ብሎኮች አራቱ እየተጠናቀቁ ስለሆነ በመጪው ሚያዚያ ወር እናስረክባለን” ብለዋል፤ የሀኮማል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ኃይሉ፡፡
አቶ ጌትነት በተለያዩ ሳይቶች በመሪ ሎቄ፣ ሲኤምሲ፣ መስቀል አደባባይ፣ ባምቢስ፣ የቀድሞው ግብርና ሚ/ር ፊት ለፊት፣ ሃያ ሁለት፣ አያት፣ ኢሲኤ፣… አካባቢዎች ፕሮጀክቶች እንዳሏቸው ጠቅሰው ፕሮጀክቶቹም በጅምር፣ በመሬት ስራ፣ መዋቅራቸው (ስትራክቸር) ያለቀ፣ ጣራ የለበሱና በመጠናቀቅ ደረጃ ላይ የሚገኙ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በስድስት መስራቾችና በ200ሺህ ብር ካፒታል በ2003 ዓ.ም የተቋቋመው ሀኮማል፤ ካፒታሉን ለማሳደግ አክሲዮን በመሸጡ በአሁኑ ወቅት ከ2000 በላይ ባለአክሲዮኖችና 60 ሚሊዮን ብር ካፒታል መሰብሰቡን፣ ገልጿል፡፡ በሁሉም የንግድ ዘርፎች ለመሰማራት የተቋቋመ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በሪል እስቴት ዘርፍ ተሰማርቶ እንደሚገኝ  አቶ ጌትነት ተናግረዋል፡፡
ሀኮማል እንደተቋቋመ ያጋጠመው ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ምን እንደሆነ አቶ ጌትነት ሲያስረዱ፣ “መንግስት ለቤት አልሚዎች መሬት በድርድር ወይም በነፃ ይሰጥ ነበር፡፡ የእኛ ድርጅት እንደተቋቋመ መሬት በሊዝ ጨረታ ብቻ እንደሚሸጥ፣ ከዚያ ውጭ ለትላልቅ የመንግስት ፕሮጀክቶች ወይም አገራዊ ጠቀሜታ ላላቸው ብቻ መሬት በድርድር ወይም በነፃ እንደሚሰጥ በማስታወቁ መሬት በድርድር፣ በነፃ ወይም በሊዝ ማግኘት አልቻልንም ብለዋል፡፡
እንዴት በሊዝ መግዛት እንዳልቻሉ ሲገልፁ፣ በሊዝ ጨረታ የሚወጡ ቦታዎች ተሸንሽነው ስለሆነ ለሀኮማል አመቺ አይደለም፡፡ ትልቁ የሊዝ ቦታ 1,000 ካሬ ሜትር ነው፡፡ ሀኮማል ትልቅ ድርጅት  በመሆኑ  ሰፊ ቦታ ይፈልጋል፡ የቢዝነስ ድርጅት ስለሆነም እነዚያን በተለያዩ አካባቢዎች የሚሸጡ ቦታዎች ገዝቶ ትርፋማ መሆን አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው በሊዝም መግዛት አልቻልንም ያልኩት፡፡ እኛ በአራት ቦታ በጨረታ ያገኘነው መሬት 1000 ካሬ ያህል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሊዝ ጨረታ የሚገዛ ቦታ ዋጋ እጅግ የጦዘበትና መንግስትም ምክንያቱን ያላወቀበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ዛሬ እንኳ አንድ ጋዜጣ ሳነብ በቦሌ ቡልቡላ ለ1 ካ.ሜ ቦታ 33ሺህ ብር ቀረበ የሚል አይቻለሁ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ዋጋ ገዝቶ እንዴት ማትረፍ ይቻላል? በማለት አብራርተዋል፡፡
ድርጅቱ መሬት በድርድር፣ በጨረታ ወይም በሊዝ መግዛት ካልቻለ እንዴት በዘጠኝ ሳይቶች ግንባታ ጀመረ? ችግር ብልሃትን ይወልዳል አይደል የሚባለው? ሌላ መላ ዘየደ፡፡ ይኸውም መሬት በሊዝ ገዝተው ገንዘብ ያጠራቸውን ባለሀብቶች ፈልጎ አብረን እንስራ አላቸው፡ ስለዚህ  እነሱ በመሬት፣ ሀኮማል በገንዘብ በጋራ እየሰሩ ነው፡፡ ከአንዱ ፕሮጀክት በስተቀር ስምንቱ በጋራ የሚያለሟቸው እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
ሀኮማል ሲቋቋም ቤቶችን በባለአክሲዮኖች ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከባንክ ብድር በመውሰድ ለመስራት አስቦ እንደሆነ የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፣ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ቅድሚያ ለመንግስት ትላልቅ ፕሮጀክቶች በመሰጠቱና የግል ባንኮችም እነዚህን ፕሮጀክቶች በገንዘብ እንዲደግፉ ስለተደረገ፣ እንዲሁም ለማኑፋክቸሪንግና ለኤክስፖርት ንግድ ካልሆነ በስተቀር ለሪል እስቴት ፕሮጀክቶች ገንዘብ ማበደር ስላልቻሉ ከባንክ ብድር ማግኘት አለመቻላቸውን ገልፀዋል፡ መጀመሪያ ላይ ደንበኛው 50 በመቶ ከከፈለ ቀሪውን 50 በመቶ ካርታውን በማስያዝ ከባንክ ጋር ብድር እናመቻቻለን ያሉት ባለመሳካቱ ለደንበኞቻቸው አሳውቀውና ተመካክረው ሌላ ዘዴ እንደፈጠሩ ተናግረዋል፡፡
ሌላው ችግር ከሁለት ዓመት በፊት በሪል እስቴት ዘርፍ የተፈጠረው ውዥንብር በእኛም ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል ብለዋል አቶ ጌትነት፡፡ ቀደም ሲል መንግስትም ሪል እስቴቶች በልማት ስም መሬት ወስደው ከማልማት ይልቅ ትንሽ ነገር አስቀምጠው መቸብቸብ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ስለነበር፣ የህዝቡንም ሆነ የመንግስትን አመኔታ ማጣታቸውን፣ እነሱ ስራቸውን በትክክል እየተወጡ ቢሆንም ውዥንብሩ እስኪጣራ ድረስ ባለአክሲዮኖች ገንዘብ በወቅቱ ያለመክፈላቸው በስራቸው ላይ ተፅዕኖ ቢያሳድርም ጠንክሮ በመስራት የደንበኞቻቸውን አመኔታ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡    
ሀኮማል በአሁኑ ወቅት የጀመራቸው ፕሮጀክቶች የ1.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሲሆን ፕሮጀክቶቹ በተለያዩ ደረጃ የሚገኙና ግንባታቸው በአማካይ ከ40 እስከ 50 በመቶ የተጠናቀቁ መሆናቸውን አቶ ጌትነት ገልጸዋል፡፡
የወደፊት እቅዳቸውንም ሲያስረዱ፣ የመካከለኛ ዕቅዳችን የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች አጠናቀን ለባለቤቶቻቸው ማስረከብ ነው፡፡ አሁን የተጀመሩት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ስለሚጠናቀቁ ከባንክ ብድር እናገኛለን የሚል እምነት አለን፡፡ የእኛ ዕቅድ በሁሉም ዘርፍ መሰማራት ስለሆነ የወቅቱን ሁኔታ እያየን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

Page 6 of 21