“በገናና ተፈጥሮ ከሌሉ ፆም ምን ይውጠዋል?” ያልኩበት ገዳም
       መቼም የዘንድሮ ጉዞዬ ውስብስብ ሆኗል፡፡ ተቃራኒ - ተስማሚ - ህብርና የማይተማመን፡፡ ጉዞ ዕውቀት የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ከጎንደር ነገሥታት ግጥም በመሠንቆ በዓል፣ ወደ መንዝ የጓሣ ብርድና ጉም፡፡ ከዚያ ከአሶሳ “ህዳሴ” ግድብ ውሃ ወደ ካይሮው ዐባይ ውሃ፣ ከካይሮ ወደ ደደቢት በረሀ (አቤት የ”ደ” ብዛቱ?! “ዴ”ን አታጥብቅ፤ “ዴዴብ” አለ ወሎዬው)፣ ከደደቢት ወደ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ ከአዋሽ ፓርክ ወደ ምሁር ገዳም - ከውሃ ወደ ውሃ፡፡ ከበረሃ ወደ በረሃ! ማን እንደ አገር!!
ባለፈው መስቀል አካባቢ ወደ ዝሙቴ ማርያም (ጉራጌ አገር) ያደረኩትን ጉዞ በመተረኬ ለጉራጌ አካባቢ አዲስ እንዳይደለሁ ትገምታላችሁ፡፡ ለነገሩ የዕድገት በሕብረት የሥራና የትምህርት ዘመቻ (አንዳንዶች ዕብደት በሕብረት ቢሉትም) በ1968 የዘመትኩት እዚሁ ጉራጌ እነሞር ነበርና ከጉራጌ አካባቢ ጋ  ትውውቄ የ40 ዓመት ዕድሜ ነው!
ጉዞውን የጋበዙን አንድ ለሴት ልጄ ሽምግልና “ልጃችሁን ለልጃችን” ሊሉ እኛ ዘንድ መጥተው የነበሩ አባት ናቸው፡፡ እኚህ አባት የምሁር ገዳም አባል ናቸው፡ ቀጭን በጣም ግልጽና ቅልል ያሉ ፣ ግርማ -ሞገሳቸው ግን በትህትናቸው ውስጥ በግልፅ የሚታይ አባት ናቸው፡
የጉዞው መነሻ ከብሥራተ ገብርኤል ነው፡፡ የተቀጠርነው በ12.30 ነው - ከጠዋቱ፡፡ የጉዞው ቀን ቅዳሜ የደብረዘይት የእኩለ ፆም ዋዜማ ነው፡፡ የእኛ አውቶብስ 1 ቁጥር ነው፡፡ ጉዞው ቁርስን፣ ምሣን እና እራትን የሚጨምር ቢሆንም ለማንኛውም ብለን ጥቂት ደረቅ ነገሮችንና ውሃ ለስንቅ ገዝተናል፡፡ አበሻ ምን ይታወቃል? ብሎ መጠራጠሩን ያውቅበታል፡፡ ሀ- ጠርጥር ነው መመሪያው፡፡
ብዙ ሰው ወደ ሣማ ሰንበት በሚሄድበት በዚህ ቀን፣ እኔ ወደ ጉራጌ አገሩ ምሁር ገዳም ነው የምሄደው፡፡ ከብሥራተ ገብርኤል የተነሳው አውቶብስ ከአለም ጤናና ከካራ ቀሪ ሰዎችን ገና ሊጭን ነው፡፡ “የአበሻ ቀጠሮ” የሚባለውን አስተሳሰብ መቼ እንደምንገላገለው አላውቅም፡፡ ከታጠቅ ጦር ሠፈር ብሥራተ ገብርኤል ለመድረስ ከንጋቱ 11 ሰዓት ከቤታቸው የወጡ ተጓዦች፤ አውቶብሱ በተባለው ሰዓት ባለመነሳቱ በጣም አማርረዋል፡፡ ዕውነታቸውን ነው፡፡ በየመንገዱ ስንቆም፣ ምግብም ሰውም ስንጭን፣ ተጠቃለን እስክንነሳ ሶስት ከሩብ ሆኗል፡፡
ዞሮ ዞሮ መሄድ አልቀረም፡፡ በሰበታ በኩል፣ ወደ ቱሉ ቦሎ አቅጣጫ ቀጠልን፡፡ ቁርስ፤ የአበሻ ዳቦ ተሰጠን፡፡ ውሃም ታደለን፡፡ የገዳም ወይም የቤተክርስቲያን ጉዞን ልዩ የሚያደርገው የሃይማኖቱን መንፈስ ብቻ ይዞ ከማያውቁት ሰው ጋር ተግባብቶ፣ ተቻችሎና ተስማምቶ መጓዙ ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ተካፍሎ አብሮ መብላቱ፣ ጨዋታ መጀመሩ፣ ከዚያ የየግል ማንነትን ማስተዋወቁ፤ በመጨረሻም ከአንድ ቤት የመጡ፣ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ያህል ተቀራርቦ መጓዙ፣ የተለመዱ የኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ጉዞ ባህሪያት ናቸው፡ የኢትዮጵያውያን ያልኩት ፈረንጆች የሃይማኖትም ሆነ የቱሪስት ጉዞ ሲያደርጉ በግለኝነት የታጠረ ጉዞ ስለሚያደርጉ ነው፡፡ እኛ ግን ነገራችን ሁሉ ጉርብትና ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ከአኗኗራችን የመነጨ ነው - neighborhood psychology ያለው ነው! ስለዚህም ያለውን ተቃምሶ ማደር ባህላችን ነው!
“አስተባባሪ” የሚመስል ነጭ በነጭ የለበሰ መልከ መልካም ልጅ አለ፡፡ “ተጓዥ” የሚል እንደ ትኬት የሚያገለግል ካርድ፣ በጥቁር ክር ማንገቻ ሰርተን አንገታችን ላይ እንድናንጠለጥል ሰጥቶናል፡፡ መንገዳችን የተሳካ ይሆን ዘንድ ለፀሎት እንድንነሳ ጠየቀ፡፡
ፀሎት አደረስን፡፡ ከአውቶብሱ ወደ ኋላ ወገን የተቀመጡት ወጣቶች፣ ሳቅ ጨዋታ የሚያዘወትሩ ዓይነት ናቸው፡፡ ወደፊት ወገን ጨመት ሰከን ያሉ ናቸው፡፡ በመጨረሻ ከዓለም ጤና የተሳፈረ ወጣት፣ ከእኛ ጐን ወደ ኋላ ቦታ በቀየረ ወጣት ምትክ አጠገባችን ተቀመጠ፡፡ ሩህሩህ ገፅታ ያለው፣ በግምት ሃያዎቹ አጋማሽ ላይ ያለ ወጣት ነው፡፡ ከባለቤቴ ጋር ለመተዋወቅ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ እሷም በተፈጥሮዋ እጅግ ተግባቢ ናት፡፡ ስለ ጉዞውና ስለ ገዳሙ ዕውቀት እንዳለው ስንመለስ ነው የገባኝ፡፡ ለእናቱ ዳቤ በሶፍት ጠቅልሎ ይዟል፡፡ ዳቤና ሶፍት አብሮ የሚሄድ አይመስልም፤ ግን እዚያ ሆነ፡፡
“የት አደርክ?” አልኩት፡፡
“ሱባዔ የገባው ጓደኛዬ ቤት” አለኝ፡፡
በዚህ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ሱባዔ መግባታቸው ገረመኝ፡፡ ከራሱ ጋር ሊነጋገር፣ ምህላ ሊገባ፣ መንፈሳዊ ዕርገት (Spiritual uplift /elevation ወይም ባሁኑ ጥበብ Transcendence of consciousness) ሊኖረው የሚፈልግ ወጣት መኖሩ አስደምሞኛል፡፡
“ሱባኤ መቼ ገብቶ ነው?”  አልኩት፡፡
“ሰኞ ዕለት ነው የመጣው፡፡ ምን ሆነ መሰለህ? ወደ ምሁር ገዳም መገንጠያው ላይ ሲደርስ የሆኑ ሰዎች አገኘና ሱባዔ ልገባ ነበር የመጣሁት፤ መንገዱ በዚህ በኩል ነወይ? አላቸው፡፡ እኛም ወደዚያው ነን አብረን እንሂድ አሉና አብረው መንገድ ጀመሩ፡፡ እዚያ ደረሱ፡፡ ለካ እሱ መሄድ የፈለገበት ሱባዔ የአቡነ መልኬ ፃዲቅ ገዳም ነው፡፡ አሁን የሄደበት ቦታ ከዚህ ገዳም የሶስት ሰዓት መንገድ ያስኬዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደ ምሁር ገዳም እንደገና የተመለሰው፡፡ እና እሱ ሱባዔ ማረፊያ ቤት ነው እኔ ያደርኩት”
“ሱባዔ የሚገባ ብዙ ወጣት አለ?”
“አዎ! እኔም ከወር በኋላ ከፋሲካ በፊት እመጣለሁ”
“በምሁር ገዳም በክብረ - በዓሉ ወቅት ሲያስተምሩ እንደሰማሁት በዓመት ሁለቴ ነው የሚከበረው፡፡ አንዱ አሁን እኛ የሄድንበት የእኩለ - ፆም/የደብረዘይት ወቅት ነው፡፡ ሁለተኛው የዕርገት በዓል ነው፡፡ ያ ማለት እንደገባኝ ከትንሣዔ በኋላ አርባ ቀን ላይ የሚከበር ነው፡፡ አይደል?”
“ትክክል ነህ፡፡ እኔ እንግዲህ ከትንሣዔ በፊት ነው ሱባዔ ልገባ ያሰብኩት” አለኝ፡፡
እንግዲህ ይሄ ከጉዞአችን ወደ አዲሳባ ስንመለስ ያወጋነው ነው፡፡ እንደተለምዶ ሳስበው ብዙ ጊዜ ከጉዞ መልስ የበለጠ ውይይትና ትውውቅ ይኖራል፡፡ የበለጠ ላላ የማለት ፈሊጥ አለው ተጓዡ፡፡ አረረም መረረም ማበሬን ተወጣሁ ዓይነት ስሜት አለ፡፡ የከዚህ ቀደሙን የሳማ ሰንበት ጉዞዬን ሳስታውስ ብዙ ሰው ለደብረዘይት እኩለ ፆም በመድረሱም ይሁን ፆሙን ማጋመስ በመቻሉ፣ እንደ የደስደስም መንፈስ አለው፤ ጠላውን፣ አረቄውን፣ አልፎ ተርፎም ቢራውን እንደ ጉድ ይጠጣዋል፡፡ ሥጋም መጠጥም ይፆም የነበረው መጠጡን ይገድፋል፡፡ አንዳች የፌሽታ ስሜት ይውጠዋል፡፡
እዚህ ምሁር ገዳም ግን ያ ሁሉ የለም፡፡ ለእኔ ዕውነተኛ ገዳም ሆኖ ነው የተሰማኝ፡፡ ሙሉ በሙሉ የአርምሞ ገዳም ሆኖ ነው ያገኘሁት - Serenity, tranquility, calmness of nature, eloquence of silence (የፀጥታ ርቱዕ - ልሣን፣ ጥሞና፣ ለሆሣሥ፣ የተፈጥሮ ዝምታ ወዘተ-- እንደማለት ያለ እርጋታ የዋጠው ከባቢ-አየር ነው፡፡
የምሁር ገዳም ጉዞአችንን ቅደም ተከተል መልከ መልካሙ ልጅ ነገረን፡፡ እሱ በተደጋጋሚ መርሃ ግብር የሚለውን ቃል ነው የሚጠቀመው፡፡ (ይሄ ቃል እኔና ባለቤቴ ስላለመድነውም ሊሆን ይችላል በመደጋገሙ አልተዋጠልንም፡፡
አንድ ወዳጄ፤ You can’t see experience but you know when it is there ያለኝ (ልምድን ቀድመህ አታየውም፤ ሲኖር ግን ታውቀዋለህ እንደማለት ነው) ልምድ ማግኘት የጉዞ ዋና አካል ነው፡፡ መንገዶች ሁሉ ሲሄዱ ረዥም ሲመለሱ አጭር ናቸው፡፡ ልምድ ይሄን ያጐናፅፈናል - ወደማናውቀው መሄድና ወደምናውቀው መመለስ፡፡
መልከ መልካሙ ልጅ፤ “ወደ ገዳሙ ልንገባ ጥቂት ሲቀረን ሃዋርያዊ ምሳ እንበላለን” አለን፣ እኛ ሃዋርያዊ ከተማን እንደምናውቅ አድርጐ ነው የሚነግረን፡፡ እሱም የልማድ ተገዢ ነው፡፡ እሱ “የምሣ መርሀ ግብር ይኖረናል” ነው ያለን፡፡ ወልቂጤን አልፈን ወደ ግራ ታጥፈን፣ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲን አየን፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ከከተሞች ራቅ ማለታቸው ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ተማሪዎች ወደ ከተማ ለመውጣት፣ ልባቸው መማለሉ ይቀንሳል፡ በአንድ ቀልብ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ/ያጠናሉ፡ ደቡብ አፍሪካ ያየሁዋቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከከተማው ራቅ ያሉ፣ ግማሽ ከተማ (Suburb) ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ግን ራሱ የዩኒቨርሲቲው ቅጽር ግቢ አንድ ከተማ ያክላል፡ ሁሉ ነገሩ የተሟላ የምሁራን አምባ ነው፡፡ በShuttle-- በትንሽ ሊዮንቺና ነው ከጫፍ ጫፍ የሚኬደው፡፡ የራሱ ቡና ቤትና የማታ ክለብም አለው፡፡ ዓርብ ዓርብ እንደ ጉድ ይደንሳሉ ተማሪዎቹ፡፡ የወልቂጤው ዩኒቨርሲቲ ይህን ያሟላ አያሟላ እንጃ፡፡
አስፋልቱን ይዘን ብዙ ከተጓዝን በኋላ ለንፋስ አቆምን። ከዚያ ወደ ኮረኮንች ገባን - ተጠምዝዘን፡፡ ሃዋርያ ከተማ ደረስን፡፡ የትምህርት ቤት ቅጽር ግቢ ነው፡ የተማሪዎቹ ደብተር በየዴስኩ ውስጥ አለ፡፡  የአገልግል ምግብ ነው፡፡ እኔ እንደተለመደው ከሳጥኑ ወጥቼ (Out of the box እንደሚሉት--- “ከመንጋው እንገንጠል” የሚለው ነው ፀጋዬ ገ/መድህን) ወደ ከተማይቱ መዓዛና ትንፋሽ ሄድኩ። ንግድ ባንክ አየሁ፤ገንዘብ ማውጣት ከቻልኩ ብዬ ጐራ አልኩ - “ጊዜ ይፈጃል ጋሼ” አለኝ። መልከ መልካሙ የጊዜ አስተባባሪያችን ደግሞ “ገና መንገድ ስላለብን ምሣ እንደጨረሳችሁ ወደ አውቶብሱ ኑ” ብሎናልና ጊዜ ከፈጀ ብተወው ይሻላል ብዬ ወጣሁ፡፡ ሱቆቹ በመቶ የተደረደሩ ጊዜ በርካታ ክርኑን ያሳረፈባቸው የሚመስሉ ናቸው። አንደኛው የጃጀ ሱቅ ገብቼ ለባለቤቴ የሞባይል ካርድ ልገዛ ጠየኩ፡፡ “ባለ 25 ብቻ ነው ያለኝ” አለኝ፡፡ ቴሌም እንደ ባንኩ ጐዶሎ ነው አልኩ፤ በሆዴ። ባለ 25 ካርድ ገዝቼ አላቅም፡፡ ግን ምን ይደረግ--ቤት ያፈራውን መብላት ነው ያበሻ ባህል፡፡ ገዛሁና ወደ አንድ ሆቴል ገባሁ፡፡ ብዙ መንገደኞች ከኛም ከሌላም አውቶብስ እዚህ ቡና ቤት አሉ፡፡ የማህበሩ ምግብ አልጣማቸውም መሰለኝ “በያይነቱ---በያይነቱ” ይላሉ፤ ምግብ ሲያዙ። ይህንን የነገርኳት አንዲት ተጓዥ፤ “እንዲያው ፆሙን የሆድ ተዝካር አደረጉትኮ! ብዙ መብላት በኋላም ገዳም ውስጥ ያስቸግራል፡፡ ለነገሩ ጥሩ ሽንት ቤት---የከተማ ዓይነት አለ፡፡ ውሃ ካፈሰሱበት ንፁህ ነው፡፡”
እቺ ደጋግማ የመጣች መሆን አለባት፤ አልኩኝ በሆዴ፡፡
“ብዙ ጊዜ መጥተሻል ወደዚህ ገዳም?”
“አሥር ዓመቴ፡፡ ለእኩለ ፆምም ለዕርገትም አልቀርም”
“ምን የተለየ ነገር አለው ገዳሙ?”
“መንፈሱ--መንፈሱ ነዋ! አቡነ መልኬ ፃዲቅ እንዲሁ አቋቋሙት?!” አለች በሙሉ - ልብ፡፡
መንፈሱን ለማዳመጥ ጓጓሁ፡፡ ደርግ፤“በጠባቧ ቢሯችን ሆነን የሰፊውን ህዝብ የልብ ትርታ እናዳምጣለን” ያለው ትዝ አለኝ በሆዴ፡፡ ሳቅ ሳቅ አለኝ፡፡
አንዳንዶቹ ስለ ማደር ይወያያሉ፡፡ “አዳራሽ ውስጥ ቦታ ካገኘን እሰየው ነው፡፡” ሌሎቹ “ድንኳንም ካገኘን ይበቃል”፡፡ አንድ አምቦሃ የሚጠጡ አዛውንት፤“መንፈሱ ካደረባችሁ የትም ብታድሩ ይሞቃችኋል!” አሉ፡፡ ሁሉም ዝም አሉ፡፡ መንፈሱ ኃይል አለዋ! ፀሐዩ የገረረ ነው፡፡ መንገዱ አቧራማ ነው፡፡ እኔ ከገባሁበት ሆቴል ማዶ ቡና አለ - የጀበና። ሰው ሁሉ ወደዚያ ይተማል፡፡ ወደ አውቶቡሱ የሚሄድ አይታይም፤ ሹፌርና ረዳትም ጭምር፡፡ ከብዙ ቆይታ በኋላ ወደየአውቶብሳችን ገባን፡፡
ገዳሙ ከሃዋርያ በጣም ቅርብ ነው፡፡ በመጀመሪያ የጠበቀን ትላልቅ ዛፍ ነው - ተፈጥሮ፡፡ የ800 ዓመት ዕድሜ ያለው ዛፍ፡፡ ብዙ የተዘመረላቸው የካሊፎርኒያ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ታላቅ ወንድም መሆን አለበት፡፡ የሚያውቅ ይኮራበታል!
ወደ ገዳሙ ቅጥር ስንገባ አሮጌ፣ በዛፍ ቅርንጫፍ የተከበበ ቤተክርስቲያንና በዚያ ትይዩ የሚታይ እስከ ማቶቱ የተገነባ ግን ያላለቀ፣ ብዙ የሲሚንቶ ሥራ የሚፈልግ አዲስ የቤተ ክርስቲያን ህንፃ አለ፡፡ ቤተክርስቲያኑን ተሳልመን፣ እያንዳንዱ በየተመስጦው ውስጥ ቆይታ አድርጐ፣ ወደቀጣዩ ዐቢይ ሥነስርዓት ሄድን፡፡ የእግር ማጠብ ሥነስርዓት!!
ሰባት አውቶብስ ህዝብ! በስልሳ ቢታሰብ ከአራት መቶ በላይ ሰው በአንድ ጊዜ በገዳሙ አባቶችና አገልጋዮች እግሩን የመታጠብ ሥነስርዓት ሊደረግለት ነው፡፡ ሴቱ ባንድ ተርታ፣ ወንዱ ባንድ ተርታ ነው፡፡ አንድ አዛውንት ናቸው የእኔን እግር ያጠቡት፡፡ ከብዶኛል፡፡ ግን የእየሱስን አርአያ ተከትለው መሆኑን አስቤ ተቀበልኩት። በጣም ደስ የሚል ስሜት አለው፡፡ ማን ይሁን ማን ሳይጨነቁ፣ ቀናም ብለው ሳያዩ እግሩን የዘረጋውን ተጓዥ ሁሉ ያጥባሉ፡፡ ጫማ አውልቆ እግር መስጠት ብቻ ነው ከእኛ የሚጠበቀው! ንፋስ፣ ዛፍ፡፡ ቤተመቅደስ። ትህትና። ብቻ ነው የሚታይ የሚሰማው፡፡ ተመስጦን ይማርካል። በመንፈስ ያንሳፍፋል፡፡   
(ይቀጥላል)

Published in ህብረተሰብ

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ለአቅመ -ሄዋን የደረሰች የደረሰች ሴት ልጅ የነበረቻቸው እናትና አባት
በአንዲት መንደር ይኖሩ ነበር፡፡
ልጅቱ ከቀን ቀን እየወፈረች ሆዷ እየሞላ ትሄዳለች፡፡ የመንደሩ ሰው ሊጠይቃቸው ሲመጣ ጥያቄው

አንድ ዓይነት ሆነ፡፡
አንዷ ትመጣና፤
“እንዴት ዋላችሁ?”
“ደህና እግዚሃር ይመስገን”
“ጤናዎትን እንዴት ከረሙ?”
“አልፎ አልፎ ይጫጫነኝና እተኛለሁ እንጂ ብዙውን ጊዜ ተመስገን ነው ጤናዬን ደህና ነኝ”
እንግዳዋ ትንሽ ታመነታና፤
“እንደው የዚች የልጅዎ ነገር እንዴት ነው?”
እናትየው እንዳላወቀ ሆነው፤
“ምኗ?”
“እንዲያው አወፋፈሯ የጤና ነው ይላሉ?”
“አይ እንዲሁ የልጅ ገላ ሆኖ ባንዴ ወፍራ ነው እንጂ ምንም የለም”
“እንደዛስ ከሆነ ደህና” ትላለች እያመነታች፡፡
ሌላዋም ትመጣና የተለመደውን የጤናና የዝምድናዋን ያህል የእግዚሃር ሰላምታ ታቀርብና፤
“እንዲያው የዚችን ልጅ ነገር ዝም አላችሁ?”
“ምኑን” ይላሉ እናት ከመሰላቸት ጭምር፡፡
“ይሄ አወፋፈሯ አላማረኝም”
“አይ የልጅ ገላ ሆኖ ነው እንጂ ምንም የለም”
“እንደዛስ ከሆነ ደህና” ትላለች እያመነታች፡፡
ሌላዋም ትመጣና የተለመደውን የጤናና የዝምድናዋን ያህል የእግዚሃር ሰላምታ ታቀርብና፤
“እንዲያው የዚችን ልጅ ነገር ዝም አላችሁ?”
“ምኑን” ይላሉ እናት ከመሰላቸት ጭምር፡፡
“ይሄ አወፋፈሯ አላመረኝም”
“አይ የልጅ ገላ ሆኖ ነው እንጂ ምንም የለም”
እንዲህ በተከታታይ ሲመልሱ፣ ለመጣው ሁሉ የልጅ ገላ ነው ሲሉ፤ እዳር ሆነው የሚያስተውሉት

አባት በመጨረሻ ተነፈሱ፤
“እናንተ ይሄን ያህል ምን አስጨነቃችሁ?
የምግብም ከሆነ ሲቀንስ እናየዋለን፡፡
የልጅም ከሆነ ሲገፋ እናገኘዋለን!” አሉና ገላገሏቸው፡፡
*   *   *
“አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንደማለት ነው፡፡ ማንኛውንም ነገር መደበቅ፣ መሸፋፈኑ አይጠቅምም - ሁሉንም ጊዜ ይገልጠዋልና፡፡ ግልፅነት ዛሬ ወቅታዊ ወረት (fashion) የሆነ ይመስላል፡፡ ስንቶች በአደባባይ እየተናገሩ ጓዳ ጓዳውን ግን የልባቸውን እንደሚሰሩ ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ They shout at most against the vices they themselves are guality of ይላሉ ፈረንጆች፡፡ “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ” እንደምንለው መሆኑ ነው በአማርኛ። ስለመልካም አስተዳደር ያወራሉ፡፡ ግን መልካም አያስተዳድሩም፡፡ ስለፍትህ ያወራሉ ግና የህግን መርህ አይከተሉም፡፡ ስለዲሞክራሲ ይናገራሉ፡፡ ግን ዲሞክራት አይደሉም፡፡ ስለእኩልነት ያወራሉ ግን ወግነው ሰው ይበድላሉ፡፡ በእኩል አያኖሩም፡፡ ስለ እጅ ንፅህና ያወራሉ፡፡ ነገር ግን እነሱ ከሙስና የፀዱ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ ግልፅነትን እንደሽፋን ነው የሚጠቀሙበት፡፡ ከእነሱ ጋር መከራከር ከንቱ ነው፡፡ አንድም “ዜጋና ሹም ተሟግቶ ደንጊያና ቅል ተላግቶ” ነው፡፡ አንድም ደግሞ ማርክ ትዌይን እንዲህ ይለኛልና፡- “ከደደብ ሰዎች ጋር አትከራከር፡፡ ወደ እነሱ ደረጃ ያወርዱህና በልምዳቸው ያሸንፉሃል” የሚለን ለዚህ ነው፡፡ (Don’t argue with stupid people, they will drag you down to their level and then beat you with experience) በትክክለኛው ሜዳ ተጫወት እንደማለት ነው፡፡ ልህነት የሌለበት ግጭት ለአደጋ ይዳርጋል፡፡ “ተምረህ ተምረህ ደንቆሮ ሆነሃል” ይላሉ መንግሥቱ ለማ፡፡ በዚያው ጽሑፋቸው:-
“አንድ ዓለም ተሰጠ ለአዳም ለሄዋን
ለሁለቱ፤ ተረቱ እንደሚነግረን
…ምንስ ልጆቻቸው ቢረቡስ ቢራቡ
ጥቂቶቹ ጠግበው ብዙዎች ይራቡ
ጥቂቶች ሲያምራቸው ያንሱ ጦርነት
ብዙዎችም ይሂዱ ለመሞት ለዕልቂት!”
ይላሉ፡፡ ስለብዙሃኑ እናስብ ዘንድ ማስገንዘባቸው ነው፡፡ ጥቂቶች በሀብት የናጠጡበት ብዙሃን ይልሱት ይቀምሱት ያጡበት ሥርዓት መቼም በጅቶን አያውቅም፡፡ የናጠጡት የበደሉ የማይመስላቸው ሲሆን ደግሞ የባሰ መደናቆር ነው፡፡ ዳቦው ሳይኖር ለሰልፉ ሲሉ ብቻ ይሰለፉ ነበር እንደሚባሉት ምስኪን ሩሲያውያን እንዳንሆን መጠንቀቅም ብልህነት ነው፡፡ ለምርጫ ዝግጅት እየተደረገበት ባለበት ባሁኑ ሰዓት፣ ተቃዋሚዎች ለአየር ሰዓትና ለበጀት በሚታገሉበት ባሁኑ ሰዓት፣ አሸናፊው ፓርቲ የለየለት በሚመስልበት ባሁኑ ሰዓት፣ ተቃዋሚዎች ጠንካራ ሆነዋል የሚል ይሆነኝ ተብሎ የተቀናጀ መንፈስ ያለበት በሚመስልበት ባሁኑ ሰዓት፣ ተሳትፈናል ማለት እንደ ድል በተቆጠረበት ባሁኑ ሰዓት፣ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ማለት በቀረበት ባሁኑ ሰዓት…ድል እንደ ዛፉ ብስል ፍሬ ስትርቅ፤ ቀበሮዋ ዘላ ዘላ ፍሬዋን መያዝና ማውረድ ሲያቅታት፤ “ለዛውም ሩቅ ናት፤ ደሞም መራራ ናት” አለች እንደተባለው እንዳይሆን ቆም
ብሎ ማሰብ ለሁላችንም ይበጀናል፡፡ ከዚህም ይሰውረን!!

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በ6 ወራት ውስጥ 100ሺ ብር ያሸልማል

  በደቦል መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽንና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) ቴሌቪዥን ትብብር የሚተላለፈው “መረዋ” የተሰኘ የድምፅ ተሰጥኦ ውድድር ሊጀመር እንደሆነ የደቦል መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን መኮንን አስታወቁ፡፡
ሰሞኑን በቤል ቪው ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ውድድሩ በዚህ ወር መጨረሻ ወይም ሚያዚያ መጀመሪያ ላይ በየሳምንቱ ቅዳሜ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሚተላለፍ ሲሆን በስድስት ወራት ውስጥ ውድድሩ ተጠናቅቆ አሸናፊው 100 ሺ ብር ይሸለማል ተብሏል፡፡
በሙዚቃ ባለሙያዎቹ በሰርፀፍሬ ስብሃትና የሺ ደምመላሽ ዳኝነት የሚካሄደው የተሰጥኦ ውድድር፤ በስድስት ወራት ተጠናቆ አሸናፊው መሸለሙን ጨምሮ፣ በድምጽ ተሰጥኦ ላይ ብቻ ማተኮሩ፣ 50 ተወዳዳሪዎች ተመርጠው በየዙሩ እየተጣሩ መሄዳቸውና ምርጥ 12ቱ ተለይተው ከታወቁበት ጊዜ አንስቶ በባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጣቸው ውድድሩ መካሄዱ ---- ልዩ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል፡፡  
አቶ ሰለሞን፣ የሺ እና ሰርፀ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በዚህ የተሰጥኦ ውድድር ላይ አንደኛ የሚወጣ 100ሺህ ብር ሽልማት እንደሚያገኝ ገልፀው፤ ከሁለተኛ እስከ 12ኛ ለሚወጡት ድምፃዊያን ዳኞችና ሌሎች እውቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች እንዲያሰለጥኗቸው ከመደረጉም በላይ ከእውቅ ባንዶች ጋር ልጆቹን በማስተዋወቅ እንዲሁም መለስተኛ ኮንሰርት በማዘጋጀት ከህዝብ እንዲገናኙና በስራ ላይ እንዲሆኑ ይደረጋል ተብሏል፡፡ “የተመዘገበ ሁሉ ለህዝብ እይታ አይቀርብም” ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ለተአማኒነቱ ሲባል ምርጥ 50ዎቹን በመለየት የመጀመሪያው የማጣሪያ ውድድር ለህዝብ  እንደሚቀርብ ገልፀዋል፡፡
ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁለቱ ዳኞች ከደቦል መልቲ ሚዲያ ጋር ባለድርሻ ሆነው ይሰራሉ ያሉት አቶ ሰለሞን፤ይህም ስራቸውን በአግባቡ እንዲወጡና ለራሳቸው ድርጅት እንደሚሰሩ አምነው እንዲተጉ ያነቃቃቸዋል ብለዋል፡፡
“መረዋ” የድምጽ ተሰጥኦ ውድድር በዚህ ወር መጨረሻ አሊያም በቀጣዩ ወር መጀመሪያ ዘወትር ቅዳሜ ከቀኑ ሰባት ጀምሮ በኢቢኤስ እንደሚቀርብ የተገለፀ ሲሆን የሙዚቃ አፍቃሪው ውድድሩን በመከታተል አስተያየቱንና ስሜቱን እንዲገልጽ የደቦል መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ባለቤትና ማናጀር አቶ ሰለሞን መኮንን ጥሪ አቅርበዋል፡፡  
  

Published in ጥበብ

WATCH ምህጻረ ቃል ሲሆን በእንግሊዝኛው (women and their children health)  የእናቶችና የልጆቻቸው ጤንነት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በካናዳ መንግስት ድጋፍ የሚደረግለት ነው፡፡ ፕላን ካናዳ እና የካናዳ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በመሆን ገንዘቡን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በጋራ ፕሮጀክቱን ሲተገብሩ ቆይተዋል፡፡ አቶ ቢንያም ጌታቸው በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የWATCH ፕሮጀክት ኮኦርዲኔተር ናቸው፡፡ የፕሮጀክቱን ማብቂያ መቃረብ ምክንያት በማድረግ ስለፕሮጀክቱ ላነሳንላቸው ጥያቄዎች የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡
ጥ/     WATCH በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ የጀመረው መቼ ነው?
መ/    የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ስራውን መተግበር የጀመረው     እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013/ጃንዋሪ ላይ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በ2015 ማርች ላይ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ውስጥ በሶስት ክልሎች ማለትም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል በሲዳማ ዞን ሠበዲኖ፣ ጎርቼ እና ቦና ዙሪያ የሚባሉ ወረዳዎች ላይ በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ እና ጢሮ አፈታ     ወረዳዎች ላይ እና በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በመቂት፣ ላስታ እና ቡግና ወረዳ     ላይ ነው፡፡
ጥ/ በዋናነት ስራው ምን ላይ ያተኮረ ነው?
መ/    ስራው በዋናነት የእናቶችን እና የሕጻናትን ጤና መንከባከብ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ እርጉዝ እናቶች በእርግዝና፣ በወሊድ እና ከወሊድ በሁዋላ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት የጤና ባለሙያዎች ሕክምናውን እንዴት መተግበር እንዳለባቸው ስልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን ድጋፋዊ ክትትልም ይደረጋል፡፡ በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮያ በኩል ደግሞ አስፈላጊው የህክምና መርጃ መሳሪያ ይሰጣል፡፡ በመጀመሪ የተደረገው በተጠቀሱት የስራ ቦታዎች ላይ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የዳሰሳ ጥናት ተካሂዶአል፡፡     ጥናቱም ያተኮረው ምን በመስራት ላይ ነው? ምን የጎደለ ነገር አለ? በምን መልክ ክፍተቱ ሊሞላ ይችላል? የሚለውን ማወቅ ሲሆን ከዚያ በሁዋላ በጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህር በኩል ምን ሊደረግ ይችላል? ፕላን ኢንተርናሽናልስ ምን ሊያሟላ ይችላል? መንግስትስ የትኛውን ክፍተት ሊሞላ ይችላል የሚለውን በዳሰሳ ጥናት ተለይቶአል፡፡ በዳሰሳው ጥናት መሰረትም Basic emergency obstetric and new born health care ወይም መሰረታዊ የሆነ የድንገተኛ፣ የወሊድና የጨቅላ ሕጻናቶች ጤና እንክብካቤ ስልጠናዎችን ለጤና ባለሙያዎች በመስጠት ነበር የተጀመረው፡
ጥ/     ስልጠናው ለምን ያህል የጤና ባለሙያዎች ተሰጠ?
መ/    በአጠቃላይ በሁሉም ወረዳዎች ወደ 48 ጤና ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን በነዚህ የጤና ጣቢያዎች ውስጥ የሚሰሩ ወደ 167/የሚሆኑ ባለሙያዎች ስልጠናውን እንዲያገኙ ሆኖአል፡፡ የሰለጠኑት የጤና ባለሙያዎች ከየጤና ጣቢያው እየተውጣጡ ሲሆን በየጤና ጣቢያውም ሶስት እና ከሶስት በላይ የሚሆኑ እድሉን አግኝተዋል፡፡ ስልጠናውም የሶስት ሳምንት ጊዜ የሚወስድ ሲሆን የመጀመሪያው ሳምንት በቲዎሪ የተደገፈ ሲሆን እንዲሁም ቀሪውን ጊዜ በሆስፒታሎች ላይ ተመድበው የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ተደርጎአል፡፡
በጅማ ዞን በጢሮ አፈታ ወረዳ ዲምቱ ጤና ጣብያ ጎራ ብለን አንዲት ወላድ አነጋግረናል፡፡ ወላድዋን ስናገኛት በጣም ጤነኛ እና ጠንካራ ነበረች፡፡ እኛ ባገኘናት ወቅት ገና ከወለደች ሰላሳ ደቂቃ የሆናት ብትሆንም እሱዋ ግን ምንም ምጥ ያማጠች አትመስልም ነበር፡፡  
“...ጠዋት ነው የወለድኩት ደህና ነኝ ጥሩ ነው ያለሁት፡፡ ከመውለዴ በፊት እዚሁ አራቴ የእርግዝና ክትትል እድርጌያለሁ፡፡ አሁንም ደህናነኝ፡፡ ...አሁን ሰባተኛ ልጄን ነው የወለድኩት፡፡ እድሜዬ አሁን ሰላሳ ሰባት አመት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ መውለድ አቆማለሁ ብዬ አስባለሁ ግን ከባለቤቴ ጋር ተነጋግረን ነው የምንወስነው...” አለች፡፡
በአካባቢው ባለው የጤና አሰራር መሰረት አንድ ለአምስት የሚባል አደረጃጀት አለ፡፡ የጤና ኤክስቴንሽኖችም አሉ፡፡ የቤተሰብ እቅድ ዘዴን በሚመለከት ይመካከራሉ፡፡ በእርግጥም  የቤተሰብ እቅድ ላይ ለመወሰን የባልየውም ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ባለቤትዋም በዚያው ባጠገብዋ ስለነበር ሀሳቡን ጠየቅነው፡፡   
“...ያው እንግዲህ ሁሉም በእግዚአብሄር ነው የሚሆነው ግን መውለድ እናቆማለን ብለን እያሰብንን ነው፡፡ ቀደም ሲል የተወለዱት ልጆች እድሜያቸው ከአስራ አራት እስከ አስራ ዘጠኝ     አመት ድረስ ነው፡፡ ሁሉም ቀበሌ ቀጄሎ ትምህርት ቤት እየተማሩ ነው፡፡ ትልቁ የአስራ ዘጠኝ     አመቱ ልጅ አሁን ሰባተኛ ክፍል ደርሶአል፡፡ አንዱ ልጅም አምስተኛ ሌላው ደግሞ     አራተኛ ክፍል ደርሶአል፡፡ እኔ በኑሮዬ ገበሬ ስለሆንኩ ልጆቼም ከትምህርት ሲመለሱ ያው ስራ ያግዙኛል፡፡ እስከአሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ንብረትም በበቂ ስላለኝ በምን አሳድጋቸዋለሁ... እንዴት እኖራለሁ ብዬ ሰግቼ አላውቅም፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉንም አሳድጋለሁ፡፡ ምናልባትም በትምህርት የሚነግሩን ነገር አለ፡፡ እሱም ምንድነው ...ሴቶች ብዙ በመውለድ ሊታመሙ ይችላሉ... የሚል ነገር ስለአለ ...ምናልባት በዚህ ምክንያት ባለቤቴ እንዳትጎዳ እያሰብኩ ነው፡፡ ስለዚህም     የወሊድ መቆጣጠሪያ እሱዋ ወይንም እኔ እንድንወስድ ወደፊት አቅጃለሁ፡፡”
ከወላድዋ እና ባለቤትዋ በሁዋላ ያነጋገርናት የህክምና ባለሙያ ሲስተር ባንቻየሁ ትባላለች፡፡ ዲምቱ ከጅማ ወደ 68/ኪሎ ሜትር እንደምትርቅ የነገረችን ሲስተር ባንቻየሁ ጤና ጣብያው በወር ከሀምሳ እስከ ስድሳ ወላዶችን እንደሚያስተናግድ እና ወላዶች ምናልባት ችግር ቢያጋጥማቸው ሪፈራል ሆስፒታሉም ጅማ ሆስፒታል መሆኑን ገልጻልናለች፡፡ ሲ/ር ሌሎች ጥያቄዎችን እንደሚከተለው ነበር ያብራራችው፡፡    
ጥ፡-  በእናቶች ጤና ዙሪያ ይሄ ቢስተካከል የምትይው ችግር አለ?
መ፡-     እናቶች አንዳንዴ በገንዘብ ላይ እራሳቸውን ቢያዘጋጁ፡፡ እሪፈር ስንልካቸው አንዳንዴ አንሄድም ገንዘብ የለንም የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ላይ እራሳቸውን ቢያዘጋጁ ወይም እሪፈር የምናደርግበት አጋጣሚ ሲኖር ከእራሳችን ከጤና ጣብያው ሰጥተን እሪፈር የምናደርግበት ነገር ቢኖር ብዬ አስባለሁ፡፡
ጥ፡- እሪፈራል ላይ ገንዘቡ ለምንድነው የሚያስፈልገው?
መ፡- በአቡላንስ ነው የምንልካቸው፡፡ እዚህ የሚያገኙት አገልግሎት በሙሉ ነፃ ነው፡፡ ግን ሆስፒታል ሲሄዱ ሆስፒታል ላይ ከግላቭ ጀምሮ እስከ መድሀኒት ለሚገለገሉባቸው ነገሮች ገንዘብ ስለሚያስፈልግ ለዛ ነው ገንዘብ የሚጠየቀው፡፡
ጥ፡- ስለዚህ አንሄድም ገንዘብ የለንም ሲሉ ምን ይደረጋል?
መ፡- አንሄድም ያሉ አንድ አምስት እናቶችን በዚህ ስድስት ወር ሰባት ወር ውስጥ ከራሳችን ገንዘብ ሰጥተን እሪፈር ያደረግናቸው አሉ፡፡ ያው ከውስጥ ገቢ ገንዘብ ላይ ተወስዶ እሪፈር ይደረጋል እንጂ አይቀርም፡፡ መሄድ ያለባቸው እናቶች መሄድ አለባቸው ብለን ከወሰንን ከእራሳችንም ቢሆን ሰጥተን ነው እሪፈር የምናደርጋቸው፡፡
ጥ፡- የአብዛኞቹ ባለቤቶች ገበሬዎች ናቸውና እሪፈር በሚላኩበት ሰአት አብረዋቸው ይገኛሉ?
መ፡- ብዙዎቹ አስቀድሞውኑ መውለጃቸው ሲቃረብ በጤና ጣብያው ተኝተው ያሉ እናቶች ናቸው፡፡ ከስምንት ወር ከአስራ አምስት ቀን የሆናቸው እናቶች እዚህ መጥተው ይተኛሉ እና አጋጣሚ ለሊትም ሆነ ቀን ባለቤታቸው ወይም ቤተሰብ በሌለበት ሰአት አንዳንዴ እሪፈር ያጋጥማል፡፡ ያው ባለቤቶቻቸው ደግሞ ከእሩቅ ቀበሌ ቢያንስ አንድ ሀያ ኪሎ ሜትር ያህል እርቀት ላይ ነው የሚገኙት... እና እነሱ ላይደርሱ ይችላሉ፡፡ አጋጣሚ የደም በጣም መፍሰስ ወይም ምጥ ላይ በሚሆኑበት ሰአት እሪፈር መደረግ ሲኖርባቸው አንዳንዴ ችግር ይገጥመናል፡፡
ጥ፡- እስከሚወልዱ ድረስ እዚህ ሲኖሩ ቀለባቸውና ሌሎች ነገሮች እንዴት ነው የሚሟሉት?
መ፡- እስከሚወልዱ ድረስ አንድ እናት ቢያንስ በቀን ሶስቴ ትመገባለች፡፡ ቁርስ ምሳና እራት ይመገባሉ ቡናም አላቸው፡፡ የእነሱን ምግብ የሚሰራላቸው ሰው አለ፡፡ ሌላው ፅዳት ነው ሳሙና ይሰጣቸዋል ፅዳታቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ምግባቸውን በትክክል ያገኛሉ ምግባቸው አይቋረጥም ችግር ካለም መጥተው ባለሙያ ያናግራሉ፡፡ መታየት ካለባቸው መጥተው ይታያሉ እና ሁሉም እንደፈለጉት ነው፡፡
ጥ፡- በጀቱ ከየት ነው የሚመደበው?
መ፡- በጀቱ አንድ ብር ለአንድ እናት በሚል ከህብረተሰቡ የሚዋጣ ብር አለ፡፡ ያ ገንዘብ እንዴት መውጣት እንዳለበት በኮሚቴ ተነጋግረን የሌለ ነገር ማለትም... ሽንኩርቱም በርበሬውም... ሁሉም እስከ ጤፍ ድረስ መገዛት ያለበት ነገር ይገዛል፡፡ ከእነሱ ጋር የሚሰበሰብ እህል ካለ  እሱንም ገቢ አድርገን አንድ ላይ ነው የምንጠቀመው፡፡
ጥ፡- ህብረተሰቡ የሚያዋጣው በፈቃደኝነት ነው ወይስ ግዴታም አለው?
መ፡- ግዴታ የለውም ፍቃደኝነት እንጂ፡፡ ሁሉም ሰው በፍላጎት አምኖበት መሆን ስለአለበት እኔም በበኩሌ በየቀበሌው እየዞርኩኝ ኮንፈረንስ ስናካሂድ ትምህርት እሰጣለሁ፡፡ ስለዚህ እያመነበት ነው ሁሉም ሰው የሚሰጠው፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ቢያንስ በሳምንት ሁለቴ መጥተው እንዲጠይቁ እንነግራቸዋለን የምናስፈርመው ውልም አለ፡፡ ማለትም እዚህ አምጥተው ጥለዋት እንዳይሄዱ እናደርጋለን፡፡   -   ይቀጥላል   

Published in ላንተና ላንቺ

ማንም ቢሆን ስደትን ወዶ አይመርጥም፤ ተገድዶ እንጂ፡፡ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በስደት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከፊሎቹ የፖለቲካ ስደተኞች፣ ከፊሎቹ ደግሞ የኢኮኖሚ ስደተኞች ናቸው፡፡ አንዳንዶች የስደት ህይወት ሳያመቻቸው ቀርቶ ከአገራቸውም ከኑሯቸውም ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ያለሙት ተሳክቶ ከራሳቸውም አልፈው ለአገር ለወገናቸው ይተርፋሉ፡፡
የዛሬው እንግዳችን ከሁለተኛው ምድብ የሚሰለፉ ናቸው፡፡ 32 ዓመት በስደት በኖሩበት አገር ሰርተውና ሁበት አፍርተው ወደ አገራቸው በመመለስ የወርቅ ማዕድን ኩባንያ፣ ትላልቅ የሕክምና መሳሪያዎች አስመጪ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት መርጃ በጎ አድራጎት ተቋም ከማቋቋማቸውም በላይ፣ በአክሲዮን በተመሰረቱ ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ በመግዛት ባለቤት ለመሆን ችለዋል፡፡
በአድዋ ከተማ ተወልደው የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያ ተከታትለው፣ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በወቅቱ የልዑል በዕደማርያም ት/ቤት አካል በነበረው “ኮሌጅ ኦፍ ቲቸርስ ኢጁኬሽን” ክፍል ተምረው በዲግሪ ተመርቀዋል - አቶ ዳዊት ገ/እግዚአብሔር፡፡
አቶ ዳዊት ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በመምህርነትና በሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) ዝግጅት ማገልገላቸውን ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ፣ ሥልጣን ላይ የነበረው የደርግ መንግስት በሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲ የተነሳ እንደፈለጉት ሰርተው ለመኖርና ኑሮአቸውን ለመለወጥ የነበራቸው ዕቅድ ሊሳካ አለመቻሉን ያስታውሳሉ። ምኞቴ ሊሳካ የሚችለው ከአገር ስወጣ ብቻ ነው የሚል ውሳኔ ላይም ይደርሳሉ፡፡ ምኞታቸውን ለማሳካት አላወላወሉም፡፡ በአስመራ በኩል አድርገው ሲገኝ በመኪና ሲጠፋ በእግር እየተጓዙ፣ ብዙም ችግር ሳያጋጥማቸው ድንበር ተሻግረው ሱዳን መግባታቸውን፣ እዚያም ብዙ ሳይቆዩ የተባበሩት አረብ ኢመሬትስ (ዱባይ) መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡
ምንም እንኳን የደርግ ሥርዓትን ለመጣል መሳሪያ አንግተው ጫካ ባይገቡም  የትግሉ አካል ነበርኩ ይላሉ፤ አቶ ዳዊት፡፡ “ትግል በብዙ መልኩ ይካሄድ ነበር፡፡ እኔ ጠብመንጃ ተሸክሜ በረሃ አልወረድኩም። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የነበረውን ስርዓት ለመጣል በተለያየ መንገድ ታግለዋል፡፡ እኔም በዚያ የትግል አካል ነበርኩ” ብለዋል፡፡
አንድ ሰው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከነበረው ኃላፊነት ተሽሮ ዝቅ ወዳለ ደረጃ ሲወረወርና በሄደበት ቦታ ሲቀናው፣ “የልምጭም ገድ አለው” ይባላል፡፡ አቶ ዳዊትም ያጋጠማቸው ነገር ተመሳሳይ ነበር፡፡ ዱባይ አልከፋችባቸውም፡፡ “ከዜጎቼ እኩል ሰርተህ መኖር ትችላለህ” በማለት እጆቿን ዘርግታ ተቀበለቻቸው። ዱባይ ገብተው ትንሽ እንደቆዩ በአንድ ነዳጅ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀመሩ፡፡ የሚገርመው ነገር በዚያ ስራ ላይ ለብዙ ዓመታት አልቆዩም፡፡
“ሜንቴናንስ ኮንስትራክሽን” የተባለ የራሳቸውን ትልቅ ኩባንያ አቋቁመው መስራት ቀጠሉ፡፡ ከዚያም ኢህአዴግ፣ ደርግን ጥሎ ሥልጣን ሲይዝ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁን መኖሪያዬ እዚህም ዱባይም ነው የሚሉት አቶ ዳዊት፤ “እዚህ ያለው ቢዝነሴ ትንሽ ነው፤ እዚያ ያለው ይበልጣል፤ ብዙ ጊዜ የቆየና የለመደም ስለሆነ እንቅስቃሴው በጣም ጥሩ ነው” ይላሉ።
አቶ ዳዊት በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የወርቅ ማዕድን አሰሳና ቁፋሮ ለማካሄድ የተቋቋመ “ዳዊት ጎልድ ማይንኒግ” የተሰኘ ኩባንያ አላቸው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ባደረጉት የማዕድን አሰሳና ፍለጋ (ሰርቨይና ኤክስፕሎሬሽን) በተወሰኑ ቦታዎች ጥሩ ውጤት እንዳገኙባቸው ገልጸዋል፡፡ 15 የውጭና የአገር ውስጥ ሙያተኞች፣ የተለያዩ ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም ወርቅ ያለበትን ስፍራ ለይተዋል፡፡ ምን ዓይነት ውጤት ይኖረዋል? በማለት ናሙናዎች በአገር ውስጥ ተመርምረውና ወደ ውጭ ተልከው ጥሩ ውጤት እንዳላቸው ስለተረጋገጠ፣ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ቁፋሮ ለመጀመር ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የወርቅ ማዕድን ምርት በካፒታልም ሆነ በባለሙያ ትልቅ አቅም የሚጠይቅ እንደሆነ የጠቀሱት ባለሀብቱ፤ አብረዋቸው የሚሰሩ ትላልቅ ኩባንያዎች እያፈላለጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላው አቶ ዳዊት ያቋቋሙት ድርጅት “ሜዲካል ፋርማ” የተባለው ድርጅት ሲሆን ከ8 ዓመት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ መንግሥት ከፍተኛ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት መኖሩን ተገንዝቦ ለመከላከል ባቀደበት ወቅት፣ ከፍተኛ የመመርመር አቅም ያላቸውን ዘመናዊ መሳሪያዎች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ በደንብ አልገቡበትም እንጂ ሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) እና ወባን መከላከልም በእቅዳቸው ውስጥ አለ፡፡
የኤችአይቪ መመርመሪያ መሳሪያዎቹ በጥራትም ሆነ በዋጋ ተመጣጣኝነት በዓለም ጤና ድርጅትና በጤና ጥበቃ ሚ/ር የተረጋገጡ ናቸው ያሉት ባለሀብቱ፤ መሳሪያዎቹን የሚያቀርቡት ለመንግስት፣ በሽታውን በግል በማከም ላይ ላሉ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች፣ በግል መመርመርና መታከም ለሚፈልጉ ግለሰቦችና መንግስታዊ ላልሆኑ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ1.1 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ የገዙት ኢንቨስተሩ፤ በራያ ቢራ ፋብሪካ የ150 ሚሊዮን ብር አክሲዮን በመግዛት ከግለሰቦች ከፍተኛው ባለድርሻ ናቸው፡፡ በናሽናል ኤርዌይስም ከፍተኛው ባለአክሲዮን እሳቸው እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
“ዳዊት ግብረ ሰናይ” በተባለው ድርጅታቸው ወላጅ የሌላቸው ልጆች የሚረዱት ባለሀብቱ፤ ከሜሪ ጆይ ጋር በመተባበር ከ50 በላይ ወላጅ አጥ ልጆችን እንደሚንከባከቡ ገልጸዋል፡፡ የገቢ አቅማቸው ደካማ የሆነ ቤተሰብ ልጆችንም ይደግፋሉ፡፡
በአድዋ፣ በአክሱምና በመቀሌ ወጣቶች በነፃ ባህልና ታሪካቸውን የሚከታተሉበት የቋንቋና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ማዕከል አቋቁመዋል፡፡ በአክሱምና በመቀሌ ግን እንደተፈለገው እየተንቀሳቀሱ አይደለም፤ በእንጥልጥል ላይ ናቸው ብለዋል አቶ ዳዊት፡፡
ባህላችንን (የአክሱም ሃውልቶች፣ አል-ነጃሺ መስጊድ…) ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ከአካባቢው ህዝብ ጋር የተነጋገርንባቸውና በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች አሉ ያሉት ባለሃብቱ፤ ከግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር ት/ቤትና ጤና ጣቢያ በማቋቋም መሳተፋቸውንና አሁንም እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “ሀብትና ገንዘብ የህሊና ደስታ የሚሰጠው ቁምነገር ላይ ሲውል ነው፡፡ እግዚአብሔር ዕድሜና ጤናውን ይስጠኝ እንጂ ገና ለመስራት ያቀድኳቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የምሰራው ለግሌ አይደለም፡፡ እኔ እንደማንኛውም ሰው በቀን የምበላው ሁለት እንጀራ ነው፡፡ ስለዚህ ለህዝብ አገልግሎትና ጥቅም በሚሰጡ ኩባንያዎች ውስጥ እሳተፋለሁ፡፡ በራያ ቢራ ፋብሪካ፣ በናሽናል ኤርዌይስ፣… ምስረታ ተሳትፌያለሁ፡፡ እንዲህ አደረግሁ ማለት ስለማልወድ ነው እንጂ ሌሎችም ይኖራሉ፡፡ ሀብት የሚገኘው አገር ሰላም ሆና፣ እግዜር ጤናና ዕድሜ ሰጥቶ መስራት ሲቻል ነው፡፡ ስለዚህ የእኔ ምኞት እነዚህን የእግዚአብሔር በረከቶች እስካገኘሁ ድረስ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ነገር መስራቴን መቀጠል ነው” ብለዋል አቶ ዳዊት ገ/እግዚአብሔር፡፡  

- ቢል ጌትስ ለ16ኛ ጊዜ መሪነቱን ይዘዋል
- ቻይና በአንድ አመት 71 አዳዲስ ቢሊየነሮችን አፍርታለች
   በየአመቱ የዓለማችንን ቀዳሚ ቢሊየነሮች ዝርዝር የሚያወጣው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ባሳለፍነው ሳምንት የ2015ን ምርጥ 500 የዓለማችን ቢሊየነሮችን ይፋ አድርጓል፡፡
ፎርብስ ለ29ኛ ጊዜ ይፋ ያደረገውን የዘንድሮ የዓለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር በቀዳሚነት የመሩት አሜሪካዊው የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ መስራች ቢል ጌትስ ሲሆኑ፣ አጠቃላይ የሃብት መጠናቸውም 79.2 ቢሊዮን ዶላር ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው አመት በነበራቸው ሃብት ላይ የ3 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ በማሳየት ለ16ኛ ጊዜ የዓለማችን ቁንጮ ባለጸጋ መሆናቸውን ያረጋገጡትን ቢል ጌትስ፣ በአመቱ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ለበጎ ምግባር በስጦታ መልክ ቢለግሱም፣ ልግስናቸው አተረፈላቸው እንጂ አልቀነሰባቸውም፡፡
እሳቸውን ተከትለው የሁለተኛነትን ደረጃ የያዙት ደግሞ፣ 77.1 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያላቸው ሜክሲኳዊው የቴሌኮም ዘርፍ ባለጸጋ ካርሎስ ስሊም ሄሉ ናቸው፡፡
ሌላኛው ስመጥር አሜሪካዊ ባለሃብት ዋረን ቡፌት በ72.7 ቢሊዮን ዶላር ሃብት የአመቱ የዓለማችን ሶስተኛ ባለጸጋ ተብለዋል፡፡
አመቱ በአለማችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቢሊየነሮች የታዩበት እንደሆነ በሚያሳየው የዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር ውስጥ፣ እስከ 500ኛ ደረጃ የያዙ በድምሩ 1826 ቢሊየነሮች የተካተቱ ሲሆን፣ አለማችን ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ብቻ 181 ቢሊየነሮችን አግኝታለች፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ለየት ባለ የኮሜዲ አቀራረቡ እውቅናን የተቀዳጀው ልጅ ያሬድ፤በየሳምንቱ ረቡዕ ከ12፡00 እስከ3፡00 ሰዓት የሚዘልቅ ስታንዳፕ ኮሜዲ በዋሽንግተን ሆቴል ማቅረብ የጀመረ ሲሆን የመጀመሪያ ዝግጅቱን ባለፈው ረቡዕ ምሽት አቅርቧል፡፡ ኮሜዲያኑ በአሜሪካ ቆይታው በተለያዩ ስቴቶችና መድረኮች ላይ ያቀረባቸው ስራዎችም በዶክሜንታሪ መልክ በአጭሩ ታይተዋል፡፡
ልጅ ያሬድ ከኮሜዲ ስራው ባሻገር የስዕል ስራዎቹንና በወዳደቁ ቁሳቁሶች የተጠበበባቸውን አስገራሚ ቅርፃ ቅርፆች በመድረክ ላይ አቅርቦ ታዳሚውን አስደንቋል፡፡ ያለፈው ረቡዕ የመክፈቻ ፕሮግራም በ“ንጉስ ፕሮሞሽን ኤንድ ኤቨንትስ” አስተባባሪነትና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ስፖንሰርነት የቀረበ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ዝግጅቱን ስፖንሰር በማድረግ ይዘልቃል ተብሏል፡፡

 በየዕለቱ የተወሰነ ስኒ ቡና አዘውትሮ መጠጣት ከደም ስር መዘጋት ችግር እንደሚታደግና በሰውነት ውስጥ ያለው የደም ዝውውር በአግባቡ እንዲከናወን በማድረግ ለልብ ህመም ከመጋለጥ እንደሚታደግ በጥናት መረጋገጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የኮርያ ተመራማሪዎች በ25 ሺህ ወንዶች እና ሴቶች ላይ የሰራውን ጥናት ዋቢ በማድረግ ዘገባው እንዳለው፣ በየዕለቱ ከሶስት እስከ አምስት ስኒ ቡና አዘውትረው የሚጠጡ ሰዎች ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ እንደሆነ ተረጋግጧል፡
ቡና በልብ ጤንነት ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በተመለከተ ከዚህ በፊት የተሰሩ ጥናቶች የተለያዩ ድምዳሜዎች ላይ እንደደረሱ ያስታወሰው ዘገባው፣ አንዳንዶቹ ቡና ለልብ ህመም ያጋልጣል ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ በአንጻሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው ማለታቸውን ገልጧል፡፡
የኮርያ ተመራማሪዎች ያወጡት የጥናት ውጤት በቡና እና በልብ ጤንነት መካከል ያለውን ትክክለኛ ግንኙነት በተመለከተ ግልጽ መረጃ እንዳልሰጠ የጠቆመው ዘገባው፣ ጉዳዩ አነጋጋሪ መሆን መጀመሩን አስረድቷል፡፡
የብሪቲሽ የልብ ፋውንዴሽን ባልደረባ የሆኑት ቪክቶሪያ ቴለርም፣ የተመራማሪዎቹን የጥናት ውጤት ለማረጋገጥና በቡና እና በልብ ጤንነት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጥራት ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ 

Published in ከአለም ዙሪያ

“የቻለ ያሸንፈኝ!”

   አሜሪካዊው ደራሲ ኤድዋርድ በቻንሪ “Brushstrokes of a Gadfly” በሚል ርዕስ በፃፈው መጽሀፉ፤ “በምርጫ ወቅት መምረጥ ካልቻልክ የሚገባህን መንግስት ታገኛለህ ይሉሀል፡፡ እውነታቸውን ነው ብለህ ስትመርጥ ደግሞ የድምጽህን ውጤት ጧ ፍርጥ ብትል እንኳ አታገኝም” ሲል የአፍሪካ ሀገራትን ምርጫ በሚገባ ገልፆታል፡፡
የቡርኪናፋሶ ህዝብ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አብሮ አደግ የልብ ጓደኛቸው የነበሩትን ፕሬዚዳንት  ቶማስ ሳንካራን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ገድለው ስልጣን ከነጠቁት ብሌዝ ኮምፓወሬ ሌላ ፕሬዚዳንት አይቶ አያውቅም፡፡ እንግሊዛዊው ደራሲ ዳግላስ አዳምስ፤ “ሰዎችን መምራት የሚፈልጉ   ለመምራት ምንም ዓይነት ብቃት የሌላቸው መሆናቸው አለም ያወቀው፣ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው” እንዳለው፣ የቡርኪናፋሶ ህዝብ ብሌዝ ካምፓወሬ አገር ለመምራት የሚያስችል የሚያወላዳ ብቃት እንደሌላቸው የተገነዘቡት ገና ከወዲሁ ነበር፡
ይሁን እንጂ ሰውየውን የጓደኛቸውን ህይወት አጥፍተው ከተቆናጠጡት የመሪነት ስልጣን ላይ ለማውረድ ከምርጫ ሌላ ምንም መሳሪያ አልነበራቸውም፡፡ እናም በ1991 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ተዘጋጅተው ጠበቋቸው፡፡ ይህንን የተገነዘቡት ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬም፤ የፖለቲካውን ምህዳርና የምርጫውን ሂደት ለራሳቸውና ለራሳቸውን ብቻ እንደሚመች አድርገው አበጃጁት። በሁኔታው እግር ተወርች ተቀይደው መንቀሳቀሻ ያጡት ተቃዋሚዎች፣ የፕሬዚዳንቱን አምባገነናዊ ድርጊት አውግዘው ከምርጫው ራሳቸውን አገለሉ። ፕሬዚዳንት ብሉዝ ካምፓወሬም ብቻቸውን በተወዳደሩበት ምርጫ ከዘጠና በመቶ በላይ ውጤት በማግኘት አሸናፊ ተባሉ፡፡
የቡርኪናፋሶ ህዝብ በነገሩ ቢከፋም ያሰበውን ከግብ ለማድረስ ተስፋ ሳይቆርጥ ቀጣዩን ብሔራዊ ምርጫ በጉጉት መጠባበቅ ጀመረ፡፡ ይሁን እንጂ በ1998 ዓ.ም የተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ እንደጠበቀው  ሳይሆን ቀረ፡፡ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ በ1991 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ወቅት ያደረጉትን ሁሉ በዚህኛው ምርጫም ላይ ደገሙት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የሰውየውን ድርጊት አውግዘው ከምርጫው ራሳቸውን በድጋሚ አገለሉ፡
የቡርኪናፋሶ ህዝብ በፕሬዚዳንቱ አምባገነናዊ ድርጊት ቆሽቱ ቢያርም የሀገሪቱ ህገ-መንግስት አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲወዳደር ስለማይፈቅድ፣ ሰውየውን በቀጣዩ ምርጫ አናያቸውም በሚል ራሱን አፅናንቶ ነበር፡፡ በ2005 ዓ.ም በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ወቅት ግን ህዝቡ ያየውን ማመን አቃተው፡፡ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ፤ ህገመንግስቱ ወደሁዋላ ተመልሶ ስለማይሰራ፣ ለሶስተኛ ጊዜ የመወዳደር መብት አለኝ በሚል ራሳቸውን በዋነኛ እጩነት አቀረቡ፡፡
ተቃዋሚዎች ጉዳዩን ለሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማቅረብ የፍትህ ያለህ ብለው አቤት አሉ፡፡ ትዕዛዙን ከፕሬዚዳንቱ በቀጥታ የሚቀበለው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደር ይችላሉ ብሎ ፍርደ ገምድል ውሳኔውን አሳለፈ፡፡
የቡርኪናፋሶ ህዝብ ይህንን ድርጊት በዝምታ ማለፍ አልፈለገም፡፡ ውሳኔውን ተቃውሞ አደባባይ ወጣ። ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬም የተቃጣባቸውን አመፅ በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱት አልሞከሩም፡፡ ይልቁንም የፀጥታና ደህንነት ሀይላቸውን አሰማርተው አመጹን በመጨፍለቅ ባለ ሀያል የብረት ክንድ መሆናቸውን አሳዩ፡፡ በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪዎችንና እንደ ኖርበርት ዘንጎ የመሳሰሉ ስመጥር ጋዜጠኞችን ሳይቀር በማስገደልና ደብዛቸውን በማጥፋት፣ በተቃውሞ የተነሱባቸውን ሀይሎች አይቀጡ ቅጣት ቀጡ፡፡
በ2006 ዓ.ም ላይም “የቻለ እስኪ ያሸንፈኝ” በሚል ለምርጫ ቀረቡ፡፡ በዚህ ምርጫ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን ለተቃዋሚ እጩዎች በመስጠቱ ከሀያ ዓመት በላይ የዘለቀው የፕሬዚዳንት ኮምፓወሬ አገዛዝ አለቀለት ተባለ፡፡ የምርጫ ታዛቢዎችም ይህንኑ መሰከሩ፡፡ የምርጫው ውጤት ሲገለጽ ግን ነገሩ ሁሉ ከታሰበውና ከተገመተው ውጪ የተገላቢጦሽ ሆነ፡፡ እንደ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሁሉ በፕሬዚዳንቱ በቀጥታ የሚታዘዘው የሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ፣ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ እጅግ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸውን ይፋ አደረገ፡፡
እስራኤላውያን ፖለቲከኞች፤ “ምርጫ ማን ወደ ስልጣን እንደሚወጣ እንጂ ስልጣን እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል መወሰን አይችልም” የሚል ምርጥ አባባል አላቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ ለሀያ ሰባት ዓመታት የዘለቀው አምባገነናዊ አገዛዛቸው ፍፃሜውን ያገኘው በህዝባዊ ምርጫ ሳይሆን በአጓጉል የስልጣን አጠቃቀማቸው ነው፡፡ የሀገሪቱ ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት ስልጣናቸውን መልቀቅ የሞት ሞት የሆነባቸው ፕሬዚዳንት ኮምፓወሬ፤ ባለፈው አመት ለአራተኛ ጊዜ መወዳደር እንዲያስችላቸው ህገመንግስቱን ለመደለዝ ሙከራ በማድረግ፣ ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጠባና አመጽ ቀሰቀሱ፡፡ ያም ህዝባዊ አመጽ ከመንበረ ስልጣናቸው ጠራርጎ በማስወገድ፣ ለአምባገነን አገዛዛቸው ፍፃሜውን አበጀለት፡፡  
ካሜሩን ከፈረንሳይና እንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ተላቅቃ፣ በነፃ ሉአላዊ ሀገርነት ከቆመች ሀምሳ አምስት አመታትን አስቆጥራለች፡፡ ላለፉት አርባ አመታት ግን ከፕሬዚዳንት ፖል ቢያ በቀር በሌላ ፕሬዚደንት ተመርታ አታውቅም፡፡ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ የነበረበትን ከ1975 እስከ 1991 ዓ.ም ያለውን ዘመን ትተን፣ የብዙኃን ፓርቲ ምርጫ ከተጀመረበት ከ1992 ዓ.ም ወዲህ ያለውን ጊዜ ብንቆጥር በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ብሔራዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡
በእነኝህ ብሔራዊ ምርጫዎች የካሜሩን ህዝብ ከፕሬዚደንት ፖል ቢያ ሌላ አሸናፊ ፕሬዚደንት አይቶም ሰምቶም አያውቅም፡፡ ፕሬዚዳንቱም በእነዚህ ሁሉ ምርጫዎች ከሠማኒያ ስምንት በመቶ ድምጽ በታች አግኝተው አያውቁም፡፡ “ስፊንክስ” በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩትን የፕሬዚደንት ፖል ቢያን ነገር ከሌሎች የተለየና ምናልባትም አስገራሚ የሚያደርገው የተካሄዱትን ምርጫዎች ሁሉ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ድምጽ ተፎካካሪዎቻቸውን በልጠው ማሸነፋቸው አይደለም፡፡ ይልቁንስ አብዛኛውን ጊዜአቸውን ከሀገራቸው ውጪ በፈረንሳይ ፓሪስ በቀን እስከ 40 ሺ ዶላር በሚከፈልበት እጅግ ቅንጡ ሆቴል ማሳለፋቸውና አንድም ቀን እንኳ ቢሆን ምረጡኝ ብለው ህዝባቸውን ቀስቅሰው አለማወቃቸው ነው፡፡
እኒህ ሰው ምርጫንና ተፎካካሪዎቻቸውን በተመለከተ ለሚቀርብላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ የሚሠጡት መልስ አጭርና ግልጽ ነበር፡ “እስኪ ከቻሉ ያሸንፉኝ!” የሚል፡፡
አምባገነን መሪዎች ምርጫ የሚያሸንፉባቸው በርካታ ህገወጥ ዘዬዎች አሏቸው፡፡ አንዳንዶቹ ህዝባዊ ብጥብጥ በማስነሳት ምርጫውን ራሱን በቁጥጥራቸው ስር ሲያደርጉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በጠራራ ፀሐይም ቢሆን የምርጫ ሳጥን ይገለብጣሉ፡፡
አንዳንዶቹ የምርጫውን ሂደት ከጅምር እስከ ፍፃሜው በመቆጣጠር ማሸነፋቸውን ሲያረጋግጡ፣ ሌሎቹ ደግሞ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ከልካይና ገዳቢ የሆኑ የምርጫ ህግና ደንቦችን በማውጣት ተፎካካሪዎቻቸውን ከምርጫ ጨዋታው በማስወገድ ድሉን በእጃቸው ያስገባሉ፡፡
የተወሰኑት ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩን አለቅጥ በማጥበብ፣ተፎካካሪዎቻቸው የእግር መትከያ አንዲትም ጋት ቦታ እንዳይኖራቸው በማድረግ፣ ሁሉንም ምርጫዎች እስከ 99.6 በመቶ የሚደርስ እጅግ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት አሸነፍን ይላሉ፡፡
ሌሎቹ ደግሞ ሁሉንም አይነት የዲሞክራሲ ተቋማት በመቆጣጠር፣ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተቀባይና አስፈፃሚ በማድረግ በከፍተኛ ድምጽ አሸናፊነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ የቡርኪናፋሶው ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ ለሃያ ሰባት አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት የተካሄዱትን ምርጫዎች ሁሉ ከላይ ከተዘረዘሩት ዘዴዎች አንዱን ወይም ሁሉንም በመጠቀም ነው፡፡
ካሜሩንን ላለፉት 40 ዓመታት የመሩት ፕሬዚዳንት ፖል ቢያ ደግሞ ተፎካካሪዎቻቸውን
“እስኪ ከቻሉ ያሸንፉኝ” እያሉ የሚዝቱባቸውና የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ እንኳ ላፍታም ቢሆን የማይጨንቃቸው በሌላ ሳይሆን የካሜሩን የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ በሌሉበት ወቅትም ቢሆን እንኳ (ለምሳሌ በ2011 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ) የምርጫውን ሂደት ከጅምር እስከ ፍፃሜው እርሳቸውን በመወከል ሳይሆን ልክ እንደ እርሳቸው ሆኖ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸውን አረጋግጦ ውጤቱን መጀመሪያ ለእሳቸው፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ለህዝቡ በይፋ ስለሚያሳውቅ ብቻ ነው፡፡
እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ኢኳቶሪያል ጊኒም የብዙኃን ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት ዘርግታለች። ስለዚህ የሀገሪቱ ህገመንግስት በሚያዘው መሰረት በየጊዜው ብሔራዊ ምርጫ ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ በምርጫው ከ95 በመቶ በላይ ድምጽ በማግኘት የሚያሸንፉት ለአራት አስርት አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚዳንት ቴወዶሮ አቢያንግ ንጉዌማ ምባሶጐ ብቻ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በ2002 እና በ2008 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ያሸነፉት 97 በመቶ ድምጽ በማግኘት ነበር፡፡
እኒህ ፕሬዚደንትም ስለ ምርጫና ስለ ተፎካካሪዎቻቸው ብትጠይቋቸው መልሳቸው አጭርና ግልጽ ነው፤ “እስኪ ከቻሉ ያሸንፉኝ” ይላሉ። ህዝቡም እኒህ መሪዎች ለምን እንዲህ አይነት መልስ እንደሚሠጡና እንዴት 99.6 ከመቶ ድምጽ አግኝተው እንደሚያሸንፉ “ነቄ” ብሏል፡፡  

Published in ከአለም ዙሪያ

በደራሲ ሃብታሙ አለባቸው የተፃፈውና በኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማሪያም ህይወት ላይ የሚያጠነጥነው “የቄሳር እንባ“ የተሰኘ ታሪካዊ  ልቦለድ መፅሀፍ ዛሬ ገበያ ላይ ይውላል፡፡ መፅሀፉ ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት ከገዙ በኋላ ከአገራቸው ኮብልለው በዚምባብዌ ሃራሬ ኑሯቸውን ባደረጉት በኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም ፖለቲካዊ ስነ ልቦና፣ ፖለቲካዊ ቁመና እና እሳቤ ላይ ጥልቅ ትንታኔ ይሰጣል ተብሏል፡፡
በ408 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ በ79 ብር ሰገበያ የቀረበ ሲሆን መጽሐፉን አሳትሞ የሚያከፋፍለው ሊትማን ቡክስ እንደሆነ ታውቋል፡፡  

Page 8 of 21