እንዴት ነው በጉዲፈቻ የተሰጠሽው?
ታሪኩ እንግዲህ የሚጀምረው ገና የ5 ዓመት ህፃን እያለሁ ነው፡፡ እናቴ በኤችአይቪ ኤድስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡ አባታችን ደግሞ ታናሽ ወንድሜ ከተወለደ በኋላ ቤተሰቡን ጥሎ በመሄዱ ከዚያ በኋላ አይተነው አናውቅም፡፡ እናታችን ስትሞት አክስታችን ወደ አዲስ አበባ አመጣችን፡፡ ለ6 ወር ከእሷ ጋር ከኖርን በኋላ እኛን የምታስተዳድርበት አቅም ስላልነበራት ትምህርት ቤት ልታስገባን አልቻለችም፡፡ የተሻለ ህይወት እንዲኖረን በማሰብም “የዘላለም ምንጭ” የተባለ ድርጅት አስገባችን፡፡ ይሄ ድርጅት ልጆችን መፅሃፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችንና ሥነ ምግባርን እያስተማረ የሚያሳድግ ነው፡፡ በዚህ ድርጅት እኔና ወንድሜ ከሌሎች ህፃናት ጋር ለ4 ዓመት ኖርን፡፡ እዚያ እያለን የዛሬ ወላጆቻችን “ኦስበርን” ቤተሰቦች በጉዲፈቻ ልጆቻቸው አድርገው ወሰዱን፡፡ እኛ ከሄድን ከ3 ዓመት በኋላ ደግሞ “የዘላለም ምንጭ” ድርጅት ውስጥ አብሮን ይኖር የነበረው ይድነቃቸው የኛን ቤተሰብ ተቀላቀለና አሁን በኦስበርን ቤተሰብ ውስጥ ሶስት ኢትዮጵያውያን አለን ማለት ነው፡፡
ስትሄጂ ደስተኛ ነበርሽ? ቅር አልተሰኘሽም?
እኛ እዚህ እያለን ሁሌም ቤተሰቦች እንዲሰጣችሁ ፀልዩ እንባል ነበር፡፡ የዛሬ አሳዳጊዎቻችንን ስናገኝ የተሰማኝ ደስታ ልዩ ነበር፡፡ ከጓደኞቻችን መለየቱ ግን በጣም ከብዶን ነበር፡፡ እዚያም ስንደርስ መጀመሪያ አካባቢ ቀላል ነበር ማለት አይቻልም፡፡ አዲስ ቤተሰብ ውስጥ ነው የገባነው፤ ባህሉ የተለየ ነው እና ለአንድ ዓመት ያህል ትንሽ ይከብድ ነበር፡፡ ነገር ግን አሳዳጊዎቻችን መልካምና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ስለነበሩ በሚገባ ተንከባክበው አላምደውናል፡፡ እናት እና አባት የሚባል ነገር ምን እንደሆነ ያወቅነው እነሱ ጋ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ቀላልና ጥሩ ነው ማለት ባይቻልም እኛ እድለኞች ሆነን መልካም ቤተሰቦች ናቸው ያጋጠሙን፡፡
በትምህርት በኩል ምን ላይ ደረሽ አሁን?
12ኛ ክፍል ነኝ፡፡ ዘንድሮ ጨርሼ ኮሌጅ እገባለሁ። ነርስ መሆን ነው የምፈልገው፡፡ ለወደፊትም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ በዚህ ሙያ ህብረተሰቡን ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ለእኔ መልካም እድል የፈጠረው እዚህ ያሉ ወላጅ አልባዎችን እንድረዳ ፈልጎ ነው ብዬ ስለማምን፣ አሁን በምማርበት ት/ቤት ሎራ ከምትባል ጓደኛዬ ጋር የገቢ ማመንጫ ዘዴ ፈጥረን እርዳታ እየሰበሰብን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ 24 ልጆችን እንረዳለን፡፡ እነዚህ ህፃናት በማደጎ ያሉ ሳይሆን የዘላለም ምንጭ ድርጅት አማካኝነት በየቤቱ የሚረዱ ናቸው፡፡
እንዴት ነው እርዳታውን የምታሰባስቡት?
እኔ የራሴን ታሪክ ለተማሪዎች እነግራለሁ። ትምህርት ቤታችን ውስጥ 2000 ተማሪዎች አሉ። ለሁሉም በቪዲዮ ኮንፈረንስ መልክ የተለያዩ ፕሮግራሞች እያዘጋጀን ስለጉዳዩ እንናገራለን፡፡ በፌስ ቡክም “Wolove” የሚል ገፅ ከፍቼ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት እርዳታ እናሰባስባለን፡፡ እስካሁን ወደ 18 ሺህ ዶላርና የተለያዩ ቁሳቁሶችን አሰባስበን ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እርዳታ አድርጌያለሁ፡፡ ለወደፊትም በዚሁ እቀጥላለሁ፡፡ ታሪኬን ስለማውቅና እግዚአብሄር እድል የሰጠኝ ይህን እንዳደርግ ስለሆነ በዚሁ እገፋበታለሁ፡፡ ለልጆቹ ቤት መከራያና የመማሪያ ገንዘብ እንሰጣለን፡፡ አሁን ለሁለት ዓመት የሚሆን በቂ ገንዘብ አለን፡፡ ለወደፊትም እርዳታ ማሰባሰቡን በተለያዩ መንገዶች እንቀጥላለን፡፡ ብዙዎች ይሄን ፕሮጀክት በጣም ስለወደዱት እየረዱን ይገኛሉ፡፡
ብዙ ጊዜ ጉዲፈቻ ተደርገው ወደ ውጪ የሚሄዱ ህፃናት በአሳዳጊዎቻቸው ተፅዕኖ ማንነታቸውን፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲረሱ ይደረጋሉ ይባላ። አንቺ ደግሞ አማርኛ አቀላጥፈሽ ነው የምትናገሪው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
እኔና ወንድሜ አንድ ቤተሰብ ውስጥ ስለገባን ስለሆነ የገባነው በአማርኛ ነበር የምንነጋገረው። አሳዳጊዎቻችንም የራሳችንን ቋንቋ እንድንጠቀም ያበረታቱን ነበር፡፡ እንግሊዝኛ የግድ የትምህርት ቋንቋ ስለሆነ ነው ለመልመድ የታገልነው፡፡ አሳዳጊዎቻችን በእንግሊዝኛ እርስ በእርስ ስናወራ እንኳን ይቆጡን ነበር፡፡ ከሌሎች አሜሪካ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር እያስተዋወቁን የሃገራችንን ባህልና ታሪክ ከነሱ እንድንረዳ ያደርጉናል። እናታችን በመንገድ ላይ ያገኘነውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሰላም እንድንልና እንድንተዋወቅ ታስገድደን ነበር፡፡
በጉዲፈቻ ተወስደው እዚያ ሃገር ችግር ላይ የወደቁ ህፃናት አልገጠሙሽም፡፡ እንዲህ ያሉ ታሪኮች ሲነገሩስ አልሰማሽም?
እኔ እዚህ ሃገር ስመጣ ነው ህፃናት ኢ-ሰብአዊ ተግባር ይፈፀምባቸዋል ነው የሚለውን የምሰማው። እዚያ እንዲህ ያለ ነገር አይሰማም፡፡ በአካባቢዬ ብቻ ከ20 በላይ የሚሆኑ የጉዲፈቻ ልጆችን አውቃለሁ፤ አንዳቸውም እንዲህ አይነት ችግር ገጥሞኛል ሲሉ አልሰማኋቸውም፡፡ አብዛኞቹ ፈረንጆች ከራሳቸውም ልጆች በላይ ለጉዲፈቻ ልጆቻቸው ስነልቦና ይጨነቃሉ። ምናልባት አንዳንድ ህፃናት ሁኔታውን ለመልመድ ይከብዳቸዋል፡፡ ወደ አሜሪካ በብዛት ጉዲፈቻ ተደርገው የሚመጡት የቻይናና የኮሪያ ህፃናት ናቸው፡፡ ሁላችንም እድለኞች ነን ብለን ነው የምናስበው፡፡
አሁን ወደ ሀገርሽ ስትመጪ ምን ዓይነት ስሜት ተፈጠረብሽ? ስለ ሀገርሽስ ምን ታስቢያለሽ?
እኔ ስመጣ ሁለተኛ ጊዜዬ ነው፡፡ መጀመሪያ የመጣሁ ጊዜ ልክ ከአውሮፕላን ስወርድ እንባ ተናንቆኝ አልቅሻለሁ፡፡ ሀገሬን በጣም እወዳታለሁ፡፡ እዚያ ሆነን ኢትዮጵያ ናፈቀን እንላለን፤ ነገር ግን ምን እንደናፈቀን አናውቅም፡፡ እዚህ ስንደርስ ግን ሁሉም ነገር ትዝ ይለናል። ስንመጣ ያሳደጉንን ዘመዶቻችንን እንጠይቃለን፡፡ በፊት የማስበው ስለራሴ ብቻ ነበር፡፡ ትንሽ ከፍ ካልኩ በኋላ ተመልሼ ስመጣ ግን ከራሴ ባሻገር ስለ ሌሎች ህፃናት ማሰብ እንዳለብኝ ተረዳሁ፡፡ ወደፊት ከኢትዮጵያ ሀገሬ መለየት አልፈልግም፡፡ በነርሲንግ ሙያ ብዙ ላበረክትላት እፈልጋለሁ፡፡ “የዘላለም ምንጭ” አሳዳጊዎቻችን ያስተማሩን ሁላችንም እንደ እህትና ወንድም ተሳስበን አብረን እንድናድግ በመሆኑ፣ በውስጣችን ይሄ መንፈስ አለ፡፡ አሁን አሜሪካ ያለነውም እዚህ ያሉትም በዚህ መንፈስ ነው የምንተሳሰበው፡፡ አሜሪካ ያለነው በየአመቱ በቀጠሮ እንገናኛለን፤ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምም እንጠያየቃለን፡፡



አሣዳጊዎችህ ላንተ ምን አይነት ሰዎች ናቸው?
በጣም ጥሩዎች ናቸው፡፡ እድለኛ ነኝ፡፡ ብዙ ነገር እያደረጉልኝ ነው የሚያስተምሩኝ፡፡ በህይወቴ የምፈልገው ደረጃ እንድደርስ የጠየኳቸውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጉልኛል፡፡ የነሱ የስጋ ልጆች አግብተው የራሳቸውን ኑሮ እየኖሩ ቢሆንም ሁሉም እንደ ታናሽ ወንድማቸው  ይንከባከቡኛል፤ ይጠይቁኛል፡፡
ስትወሰድ ምን ዓይነት ስሜት ነበር የተፈጠረብህ?
ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም አዲስ ህይወት አዲስ አለም እንደማይ አስብ ነበር፡፡ የእናትና አባት ፍቅር ምን እንደሆነ ለማወቅም እጓጓ ነበር፡፡ ሁላችንም ወላጅ አልባዎች ቤተሰብ እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡ ሌሎች ልጆች ያላቸውን ነገር ሁሉ እንዲኖረን እንሻለን፡፡
አዲሶቹን አሣዳጊዎችህን ለመላመድ አልከበደህም?
ብዙም አልከበደኝም፡፡ እነሱ ጥሩ ፍቅርና እንክብካቤ ያደርጉልኝ ስለነበር እንደዚያ ዓይነት ችግር አልገጠመኝም፡፡ ነገር ግን እዚህ ያሉት ጓደኞቼ ይናፍቁኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን እየለመድኩ ስመጣ፣ ትኩረቴን ሙሉ ለሙሉ ወደ ትምህርቴ ለማድረግ ችያለሁ፡፡ ቤተሰቦቼም እንደ ልጃቸው ነው የሚያዩኝ። እንደውም ትንሽም ያቀብጡኛል። ሞባይልና መኪና ከልጆቻቸው በፊት ነው ለኔ ገዝተው በስጦታ ያበረከቱልኝ፡፡
የወደፊት ህልምህ ምንድን ነው?
ኢንጅነሪንግ ወይም ኢንተርናሽናል የቢዝነስ ትምህርት ተምሬ ኢትዮጵያን ማገልገል እፈልጋለሁ። ሀገሬን መርዳት ከቻልኩ ለኔ ትልቁ ደስታዬ ነው። በአሜሪካውያን አሣዳጊዎች እያደግሁ አሜሪካ ብኖርም ኢትዮጵያዊ መሆኔን መቼም አልረሣውም። ድሃ ነበርኩ፤ እግዚአብሔር ከፍ አድርጐኛል፡፡ ድሃ የሆኑትንም እግዚአብሔር ከፍ እንዲያደርጋቸው እየፀለይኩ ብዙዎችን በማደጐ ወስጄ የመርዳት እቅድ አለኝ፡፡
እዚህ ከመጣህ በኋላ ዘመዶችህን አገኘህ?
ዘመዶቼ ናፍቀውኝ ስለነበር ሳገኛቸው በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እነሱም በጣም ደስ ብሏቸዋል። እነሱን ሳያቸው ለካ አሜሪካ መሄዴ ከነሱ የተሻለ እንድኖር ነበር የሚል ስሜት ተሠምቶኛል፡፡ እግዚአብሔር ከፈቀደ እነሱንም የመርዳት ሃሳብ አለኝ፡፡
በጉዲፈቻ ተወስደው የማንነት ቀውስ የገጠማቸው ኢትዮጵያውያን ህፃናት የሉም?
የማንነት ቀውስ የሚገጥማቸው ልጆች፣ ችግሩ የሚመነጨው ከመሠረታቸው ነው ፡፡ ከዚህ ሲሄዱ ትንሽ ስለ ጉዲፈቻ ምንነት እንዲያውቁ ቢደረግ ችግሩ አይገጥማቸውም፡፡ ከኢትዮጵያ ሲሄዱ ቆዳቸው ተገፎ አሜሪካዊ የሚሆኑ የሚመስላቸው ከሆነ ግን የማንነት ቀውስ ይገጥማቸዋል፡፡ አሜሪካዊ ለመሆን መሞከር ራሱን የቻለ ስራ ነው፤ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ግን ቀላል ነው፡፡
*       *        *
ሁለቱም የጉዲፈቻ ልጆች በዚህ ጉዳይ ይስማማሉ። “እኛ አሜሪካዊ እንሁን ብንልም አንችልም፤ ኢትዮጵያዊ ደማችን የት ሄዶ?...” ነገር ግን በጉዲፈቻ መሠጠታችን ለህይወታችን መልካም እድልን ከፍቶልናል፡፡ ሰዎች እንደሚያስቡት ሳይሆን የወላጅ ፍቅር አግኝተን ህይወታችን የተሟላ ሆኖልናል፡፡ ጉዲፈቻን ጨለማ ብቻ አድርገን አንየው” ብለዋል፡፡
ታዳጊዎቹን ከአሳዳጊዎች ጋር ያገናኘው “የዘላለም ምንጭ”፤ ዛሬ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ላይ የሚሠራ ሲሆን ወደ 1500 የሚሆኑ ችግረኛ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው እንዲረዱ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን አሣዳጊዎች እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አቶ ነሲቡ ከበደ ይገልፃሉ፡፡ በአሁን ሰአትም ድርጅቱ ራሱን አሳድጐ ሰበታ አካባቢ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ለመገንባት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

Published in ህብረተሰብ

እሑድ፦ በዓለ ትንሣኤ ሲሆን ። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ሦስት ሌሊት ሦስት መዓልት በከርሠ መቃብር አድሮ መነሳቱን የምናስታውስበትና የመስቀል መርገምነቱ ቀርቶ ትንሣኤነቱ የታወቀበት፤ ሙስና መቃብር የተሻረበት ትንሣኤያችንን በትንሣኤው ያረጋገጥንበት ዕለት ነው።
ሰኞ፦ ፩ኛ ማዕዶት ይባላል።
ማዕዶት ማለት (መሻገሪያ፣ መሻገር) ማለት ነው። ምሳሌው ቀድሞ እስራኤላውያን ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው ምድረ ርስት ገብተዋል። ምሳሌውም ፈርዖን የዲያብሎስ፣ ሠራዊቱ የሠራዊተ ዲያብሎስ፣ ግብፅ የሲኦል፣ ባሕረ ኤርትራ የባሕረ ሲኦል፣ እስራኤል የምእመናን፣ ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር፣ በትረ ሙሴ የመስቀል ምሳሌ እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ተሻግረው ምድረ ርስት እንደገቡ ነፍሳትም በክርስቶስ መሪነት ባሕረ ሲኦልን ተሻግረው ገነት የመግባታቸው ምሳሌ ነው። በዚህም ማዕዶት ይባላል።
፪ኛ ዕለተ አብርሃም (ዕለቱ ለአብርሃም) ይባላል። አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከነዓን ገብቷል። በዚህም አንጻር ምእመናንም ባሕረ ሲኦልን ተሻግረው ገነት የመግባታቸው ምሳሌ ነው። አንድም አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሄድ መልከጼዴቅ ኅብስተ አኰቴት ጽዋዐ በረከት ይዞ ተቀብሎታል። ነፍሳትም ባሕረ ሲኦልን ተሻግረው ቢሄዱ ኅብስተ በረከት ጽዋዐ አኰቴት ወልድን የማግኘታቸውና ወደ ቀድሞ የበረከት ርስት የመመለሳቸው ምሳሌ ነው። ስለዚህ ትንቢቱ ምሳሌው መድረሱን ለማጠየቅ ዕለቷ ማዕዶት ትባላለች።
ማክሰኞ፦ ቶማስ ይባላል።
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የጌታችንን ጐን የዳሰሰበትና እጁ የደረቀችበት እንደገና መልሳ የዳነችበት መታሰቢያ ነው። ለቶማስ ታሪክ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ዕለቱ ቶማስ ይባላል። ምንም እንኳን ታሪኩ የዳግማይ ትንሣኤ ቢሆንም አበው ታሪክ ከታሪክ እንዳይደራረብ ብለው ነው። ዩሐ20፤27-29
ረቡዕ፦ አልዓዛር ይባላል። ዮሐ ፲፩፥ ፵
አልዓዛር ጌታችን በጥንተ ስብከት ያስነሳው ሲሆን ታሪኩ በዮሐንስ ወንጌል በሙሉነት ተመዝግቧል። ከሞት የተነሳው መጋቢት ፲፯ ቀን ነው። በዚሁ ቀን መታሰቢያ እንዳያደርጉለት የግርግር ወራት ሆነ በ፳፪ም ሆሳዕና ሆነ፤ በ፳፫ም ርግመተ በለስ አንጽሖ ቤተ መቅደስ ሆነ በዓሉ ከበዓል ይዋል ብለው አበው የውኃ በዓል ከውኃ ብለው ቃና ዘገሊላን ከጥምቀት ጥግ እንዳዋሉ ትንሣኤው ከትንሣኤ ጋራ እንዲሄድ አደረጉ። አንድም አልዓዛር በትንሣኤ ሥጋ እንደተነሣ እኛም ትንሣኤ ልቡና፣ እንነሣለንና።
ሐሙስ፦ አዳም ይባላል። የአዳም ምሉዕ ተስፋ የተፈጸመለትን ምስጢር የምናስታውስበትና የምንዘክርበት ዕለት ነው። ምክንያቱም ለክርስቶስ ሰው መሆን ዋና ምክንያቱ ጸሎተ አዳም ወሔዋን ስለሆነ ርደተ ሲኦልን በሚጠታቸው፣ ርደተ መቃብርን በሙስና መቃብር፣ ጽልመተ ሲኦልን በብርሃነ መለኮት ለውጦ ሞተ ሥጋ ወነፍስ ተፈርዶባቸው የነበረው ሁሉ አልፎ “ኃጢአት ከበዛችበት ዘንድ ጸጋ እግዚአብሔር ትበዛለች” ብለው ያመሰገኑበት መታሰቢያ ስለሆነ፤ አዳምና ሔዋን ከሲኦል የወጡት ዓርብ ሲሆን እዚህ መከበሩ ለምንድ ነው ከተባለ ዓርብ ለበለጠው ለአምላካቸውና ለአዳኛቸው ለክርስቶስ ስቅለት ስለሆነ በዚሁ ዕለት ይከበራል። ያውስ ይሁን ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ አለመዋሉ ሐሙስ መዋሉ ለምንድ ነው ቢሉ፥ ከእሑድ እስከ ሐሙስ አምስት ቀን ይሆናል። አምስት ከእኩል ሲፈጸም አድንሃለሁ ብሎት ነበርና ያ እንደተፈጸመ ለማጠየቅ ነው።
ዓርብ፦ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች። ጌታችን ከልደቱ እስከ ሞቱ ያደረገው የማዳን ጉዞ በሙሉ የተፈጸመው ዓርብ ነው። “ወይቤ ተፈጸመ ኵሉ” እንዲል። ዓርብ የቤተ ክርስቲያን ሁለመናዊ ምስጢር የተፈጸመበት ዕለት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች። ማለትም ዓርብ ለቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆኑ ዋና ዋና ምስጢራት ተሟልተዋል። ለምሣሌ የመስቀል አዳኝነቱ ከእርግማንነቱ ተለይቶ ታውቋል፤ የሕንጻዋ መሠረት ቀራኒዮ ተተክሎላታል፤ ሥጋ መለኮት የምትፈትተው በቀራኒዮ ተቆርሶላታል፤ ልጆቿን ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ ገቦ ፈስሶላታል። ስብከት፣ ትምህርት፣ ተአምራት፣ ትንሣኤ ተደርጎላታል። ይህንን ሁሉ ምሥጢር ያገኘችው በዕለተ ዓርብ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ተባለች። የዓርብ ትርጓሜው የሥራ መክተቻ፣ ምዕራብ፣ መግቢያ ማለት ነውና። ኤፍ2፤19፤ራዕ1፤6-8
ቅዳሜ፦ አንስት አንከራ ትባላለች። በዕለተ ትንሣኤ ሌሊቱን ሲመላለሱ ያደሩ ሴቶች የድካማቸውና ጌታን የመሻታቸው ዋጋ መታሰቢያቸው ነው።
አንስት አንከራ መባሉ ሌሊት ሲመላለሱ ሁለት መላእክት አይተው ከብሩህነታቸው የተነሳ የተደነቁበትና በመቃብሩ ያለውን መዓዛ ትንሣኤ አሽትተው የተመሰጡበት ዕለት ስለሆነ እንዲሁም ድካማቸው ከንቱ እንዳልሆነ ለማጠየቅ ነው። አንድም ጌታችን አስቀድሞ ለእነርሱ ታይቶ ትንሣኤውን ያረጋገጠበት ስለሆነ እነርሱ ከአምላክነቱ ግርማ የተነሳ ረቡኒ ብለው ያደነቁበት ዕለት መታሰቢያ ስለሆነ። አንድም በጠቅላላው ከሕማማቱ እስከ ትንሣኤው ብዙ የእንባ መሥዋዕት ያቀረቡ እናቶች የሚታሰቡበት ስለሆነ አንስት አንከራ ይባላል።
እሑድ፦ ዳግም ትንሣኤ ይባላል።
ዳግማይነቱ ጌታችን ሳምንቱን ተሰውሮባቸው ሰንብቶ በዝግ ቤት እያሉ ዳግመኛ ስለተገለጸላቸው ዳግም ትንሣኤ ይባላል። ውስጠ ምሥጢሩ ግን ከእሑድ ከቀዳማይ ትንሣኤ ጀምረው ቢቆጥሩ ስምንት ቀን ይሆናል። አንድ ቀን እንደ አንድ ሺሕ ቆጥሮ ስምንት ሺሕ ይሆናል። ዳግማይነቱ ለትንሣኤ ነውና በስምንተኛው ሺሕ ዘመን ዳግም በትንሣኤ ዘጉባኤ እንነሣለን ለማለት ዳግም ትንሣኤ ተባለ።

Published in ህብረተሰብ
Monday, 20 April 2015 15:38

የጥረት ፍሬ

ወ/ሮ ውድነሽ መልከ መልካምና የደስደስ ያላት፤ ሳቂታና ተጫዋች ናት። በልጅነቷ ገበያ ላይ ከተዋወቀችዉ ጓደኛዋ ጋር ትዳር መስርታ አንድ ልጅ አፍርተዋል። ከእለታት በአንዱ ቀን ጨለማ ለብርሃን ስፍራዉን ሲለቅ ተነስታ ለባለቤቷ ቁርስ ታዘጋጃለች። ባለቤቷ ደግሞ ቀን ለሚሰራቸዉ ስራዎች የሚያስፈልጉትን ነገሮች ካዘጋጀች በኋላ ቁርሳቸዉን በፍቅር አብረዉ ተመገቡ። ከቁርስ በኋላ ባለቤቷ ሲለባብስ ይንን ልበስ፣ ይህንን ቀይር፤ እዚህ ጋር አስተካክል እያለች ካቆነጃጀችዉ በኋላ የግራ እጆቿን ጣቶች የቀኝ እጆቹ ጣቶች ውስጥ አሰካክታ ከቤት ይዛው ወጣችና እሱ ወደ መኪናው ሲሄድ ቆም ብላ እጆቿን ከእጆቹ በቀስታ አላቀቀች። መኪና ውስጥ ገብቶ ሲያስነሳ ሰራተኛዋን ጠርታ የግቢዉን በር እንድትከፍትለት ነገረቻት። ሰራተኛዋ በሩን ከፍታ ወደነሱ ስትመለከት ወ/ሮ ውድነሽ ጠጋ ብላ ባለቤቷ የለመደዉን የስንብት ሰላምታ ለማግኘት ዝቅ ባደረገዉ መስታወት በኩል ሳም አድርጋዉ በፍቅር ተሰናበተችዉ። ይህን የተመለከተችዉ ሰራተኛዋ በቀኝ እጇ አፏን እንደመሸፈን ብላ በማፈር መንፈስ ወደ መሬት አቀረቀረች።  ባለቤቷ አቶ ወርቅነህ ግቢውን ለቆ ሲወጣ ወ/ሮ ውድነሽ በሩን ዘግታ ከሰራተኛዋ ጋር ወደ ቤት ተመለሱ።
ሰራተኛዋ የተለመደውን አልጋ የማንጠፍ፣ ቤት የማጽዳት፣ እቃ የማጣጠብ ስራዋን ጨርሳ ወደሚቀጥለዉ ምግብ የማብሰል ስራዋ ልትሄድ ስትዘጋጅ ስትመለከታት የነበረችዉ ወ/ሮ ውድነሽ አንዳች ነገር ልቧን ደቃትና “ፈለጉሽ ነይ እሰኪ!” ብላ ወደራሷ ጠራቻት። ሰራተኛዋ ስራዎቹን የምትሰራዉ በግዴለሽነት ነዉ። በህይወቷ ለማሳካት የምትፈልገዉ ምንም አይነት ህልም የላትም። ያላትን መልካም አጋጣሚዎች ሁሉ ሳትጠቀምባቸው ታባክናለች። ገና ከገጠር ወደ ከተማ ስትመጣ  በአንዳንድ ጓደኞቿ እና አጉል ተስፋ በሚሰጡ ሰዎች ተገፋፍታ ትምህርቷን ቤተሰቧ ጋር ሆና በአግባቡ ትምህርቷን እየተማረች ካለችበት አቋርጣ የመጣችዉ። አሁን ደግሞ ያቋረጠችዉን ትምህርቷን ማታ ማታ እንድትቀጥል ወ/ሮ ውድነሽ ከስራ ነጻ በማድረግ ሁኔታዎችን ብታመቻችላትና ብትገፋፋትም ፈቃደኛ አልሆነችም። የምትሰራበትን ገንዘብ እንኳን አጠራቅማ እራሷን ለመለወጥ አትጥርም። ‘የማይረቡ ነገሮችን’ በመግዛት አበካክና ትጨርሳለች። እናም ወ/ሮ ውድነሽ ሁሌ ትመክራታለች፤ እሷ ግን መስማት እንጂ ወደተግባር ስትለውጥ አትታይም። በዚያን እለት ግን ትምህርት እንዲሆናት ብላ የራሷን የልጅነት ልፋት ኮስተር ባለ መንፈስ እንደተሞክሮ አካፈለቻት።
“ይኸዉልሽ ፈለጉሽ፣ ነገ የተሻለ ህይወት ለመኖር ዛሬን መጣጣር ያስፈልግሻል። እኔ ከወላጆቼ የወረስኩት ገንዘብና እውቀት አልነበረም። ስለዚህም ገና ትንሽ ልጅ እያለሁ ኑሮዬን የተሻለ ለማድረግ በሰፈር ውስጥ ድንች፣ ቃሪያ፣ ሽንኩርት፣ጎመን…የመሳሰሉትን እየቸረቸርኩ ለራሴ የሚያስፈልጉኝን አንዳንድ ነገሮች እገዛ ነበር። በዚያ ሂደት ከጊዜ በኋላ ትንሽ ብር ማጠራቀም ቻልኩኝ። ያጠራቀምኩትን ብር ይዤ የቻለልኝን ያክል እቃ ገዝቼ እያዞርኩ ሱቅ በደረቴ መስራት ጀመርኩኝ። ስራዉን እየሰራሁ የበለጠ ገንዘብም እያገኘሁ እያለ አንድ ቀን …” እንዳለች ትካዜ ውስጥ ገባችና ንግግሯን አቋረጠች።
“እንዴ እትዬ ምነው ቆዘሙሳ?” አለቻት ሰራተኛዋ።
ለሴኮንዶች ጸጥ ካለች በኋላ “አይ ምንም አይደለም” ብላ ጨዋታዋን ቀጠለች። “እ…በእለቱ የእግረኛ መንገድ ዘግተን እንዳንሸጥ ፖሊስ ሲያባርረን ለማምለጥ የመኪና መንገድ እያቋረጥኩ ስሮጥ ከባድ የመኪና አደጋ ደረሰብኝ። በዘመድ አዝማድ ድጋፍ ጭምር ህክምና ባገኝም ከልጅነቴ ጀምሮ ከግራ እጄ ጋር ጉዳት የነበረበት የቀኝ እግሬ ከአገልግሎት ውጪ ሆነ” ብላ እምባ እየተናነቃት በአውራ ጣቷ እና በአመልካች ጣቷ ሁለት ዓይኖቿን ከድና ይዛ ወደታች አቀረቀረች።
“አይዞት እትዬ፤ እግዚአብሄር ይማሮት” አለቻት ሰራተኛዋ በሀዘኔታ።
“አዎ ምሮኛል!” ብላ ቀና አለችና ጨዋታዋን ቀጠለች ወ/ሮ ውድነሽ። “ታዲያ ያን ጊዜ ተስፋዬ ጨልሞ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ባላወኩበት ጊዜ የአማራ ክልል የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ፍላጎት ላላቸዉ ሴቶች መጠነኛ ብድርና የመስሪያ ቦታ እንደሚያመቻቹ ሰማሁ። በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ጉዳዩን ማጣራትና መከታተል ያዝኩኝ። በመጨረሻም በአካል ጉዳተኝነት ቅድሚያ እድሉን በማግኘቴ ተስፋዬ አንሰራርቶ  መደብ ይዤ እጉልት የንግድ ስረዬን መስራት ጀመርኩኝ። ከዚያ ጊዜ በኋላ የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች ሁሉ በጽናት በማለፍ ይኸዉ ለዚህ በቅቻለሁ። አንቺም ነገ ኑሮሽን ለመቀየር ዛሬ መጣጣር አለብሽ” ብላ አጠንክራ ነገረቻት።
“እሺ እትዬ፤ እጥራለሁ!” አለች ሰራተኛዋ።
እናትና አባት ወደ ባህር ዳር የመጡት የእድሜያቸውን እኩሌታ ካሳለፉበት የደቡብ ጎንደር ገጠራማ አካባቢ ሲሆን ወ/ሮ ውድነሽ ግን የተወለደችዉ ባህረ ዳር ነው። ከመጻፍና ማንበብ ያለፈ ምንም ትምህርት አልተማሩም። በሚያባትል የኑሮ ውጣውረድ ተጠምደዉ እላይ እታች ዱብዱብ ሲሉ የኖሩ ናቸው። አባቷ የቀን ስራና ያገኙትን ተባራሪ ስራ በመስራት ህይወትን ሲመሩ የኖሩ ሲሆን እናቷ ደግሞ የሰው ቤት በተመላላሽ ሰራተኝነት እና በሰፈር ውስጥ ልብስ በማጠብ በሚያገኟት ገቢ ኑሯቸዉን ሲደጉሙ የኖሩ ናቸው።
ወ/ሮ ውድነሽ ታዲያ በልጅነቷ ወደ ትምህርት ቤት እንድትገባ ከወላጆቿ ሁኔታዎችን የማመቻቸትም ሆነ የመገፋፋት እድል አልገጠማትም። ‘ከጓደኞቼ አልቀርም’ እያለች በማልቀስ  እና ብሶ ሲመጣም ‘ከጓደኖቿ በታች አታድርጓት’ እያስባለች በጎረቤቶቻቸው በማስነገር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃለች። ከቤት ሳትወጣ የቤት ውስጥ ስራ ብቻ እንድትሰራ ነበር የቤተሰቦቿ ፍላጎት። ‘ሴት ልጅ በማጀት ውላ የቤት ዉስጥ ስራ ብቻ ስትሰራ ተፈላጊነቷ ይጨምራል፤ ከቤት ወጥታ አደባባይ ከዋለች ግን እሷ አለሌ ናት እየተባለች ተፈላጊነቷ ይቀንስና ቆማ ትቀራለች’ የሚለው ለዘመናት በህብረተሰቡ ውስጥ ሰርጾ የቆየ አባባል በወ/ሮ ውድነሽ ቤተሰቦችም ዘንድ የጸና ነበር። ከዚህ ሌላ ደግሞ አካል ጉዳተኛ በመሆኗ ብዙ የእድሜ እኩዮቿ ይርቋት ስለነበርና የአካባቢዉ ሰዎችም በተለየ ሁኔታ ያይዋት ስለነበር ‘የተረገመ ዘር አለባቸዉ’ ብሎ ህብረተሰቡ እንዳያገላቸዉ በመስጋትም ጭምር ነበር ከቤት እንዳትወጣ ጥረት ያደርጉ የነበረዉ። ሌላው ቀርቶ እንግዳ ወደ ቤታቸዉ ሲመጣ እንኳን ፊት ለፊት እንዳትታይ ወደጓዳ እንድትገባ ያደርጓት ነበር።
ሰራተኛዋን ለመምከር ካደረገችዉ ጥረት በኋላ ያለፈዉ መጥፎ ትዝታ መንፈሷን ስለረበሸዉ ወ/ሮ ውድነሽ ትንሽ እረፍት ለማግኘት ባለ አንድ ፎቅ የሆነው ቤታቸው አናት ላይ ወዳለዉ ክፍት ቦታ ወጥታ አረፍ አለች። ባለችበት ሆና ግቢዉን በዓይኗ መቃኘት ጀመረች። ግቢያቸዉ በጣም ሰፊና የተዋበ ነው። በልዩ ልዩ አበባ እና በተፈጥሮ ሳር ፈርጅ ፈርጅ ባለው መልኩ የተሸፈነ ነው። እጸዋቱ ለዓይን ከመማረካቸዉ ባሻገር ግቢውን ነፋሻማ አድርገዉታል። ከውሻ ቤት ጀምሮ በግቢዉ ውስጥ ያሉ ክፍሎች በንጽህና የተያዙ ናቸዉ።  
በዓይኗ ግቢዉን እየቃኘች ሆዷ ውስጥ የሆነ ስሜት ተሰማት። ወዲያዉ በኋላ ባለቤቷ አቶ ወርቅነህ ትዝ ላት እና ለራሷ ፈገግ አለች። አንድ ቀን ከዋለበት የንግድ ስራዉ ሲመጣ ወ/ሮ ወድነሽን አልጋ ላይ አገኛት። በቀስታ ወደ እሷ ካመራ በኋላ፤
“የኔ ውድ፤ ስላም ዋልሽ?” ብሎ በፍቅር ሳም አደረጋት።
“ደህና ነኝ” አለችዉ በደንብ እየነቃች።
ወደታች ወረድ ብሎ ሆዷን ዳበስ እያደረገ “እንዴት ነው ይህ ጎረምሳ?” አላት።
ሳቅ እንደማለት ብላ “ጎረምሳ መሆኑን እንዴት አወቅክ? ጎረመሲት ናት!” አለችዉ እና ሁለቱም ተያይተዉ ተሳሳቁ።
ወ/ሮ ውድነሽ ድርስ ናት። ካረገዘችበት ጊዜ ጀምሮ የምታሳያቸዉ በየጊዜዉ ስሜቶቿ ይቀያየራሉ። እርግዝናዉ ከአካል ጉዳተኝነቷም ጋር ተዳምሮ ጫና እንዳይፈጥርባት አቶ ወርቅነህ አጥብቆ ከጎኗ በመሆን የምትፈልገዉን ሁሉ አቅሙ በፈቀደዉ መጠን በማሟላትና በመንከባከብ የድረሻዉን ይወጣል።
በዚያች ቅጽበት በሃሳብ ሰረገላ እየጋለበች ከባለቤቷ ጋር ያሳለፈቻቸውን መልካም ጊዜ በዓይነ ህሊናዋ መቃኘት ጀመረች።
ሁለቱም አብረዉ ብዙ ጊዜ በእግር ጉዞ የደርጉ ነበር። ከእለታት በአንዱ ቀን አመሻሽ ላይ የእግር መንገድ ለማድረግ ተያይዘዉ ወጡ። በእለቱ የእግር ጉዞውን ለማድረግ የወሰኑት ለቤታቸዉ ቅርብ ወደሆነው ጣና ሃይቅ ዳርቻ በመሆኑ ወደዚያዉ ተጓዙ። የሃይቁ ዳርቻ ሸክላማ ድንጋይ የተነጠፈ በመሆኑ ለአግር ጉዞ በጣም ተመችቷቸዋል። ከመንገዱ በቀኝ በኩል ሃይቁን ተንተርሰዉ በተሰሩ የሃይቅ ዳርቻ መዝናኛዎችና ለምለም እጸዋት አይናቸዉ ተማርኳል። ወደ ግራ ዞር ሲሉ ደግሞ  ሃይቁና ሰማዩ የተገናኙበት የሚመስል ቦታ ላይ በግማሽ የጠለቀችው ፀሐይ በቀረዉ አካሏ በምትለቀዉ ፍም እሳት በሚመስለዉ ብርሃኗ የውሃው ገጽ ላይ የተለየ ማራኪ ሁኔታን ፈጥራላቸዋለች። በስፍራዉ በሚታየዉ ነገር በሙሉ መንፈሳቸዉ ታድሷል። ለእግር ጉዞዉ ከተነጠፈዉ ሸክላማ ድንጋይ መጨረሻ ሲደርሱ ከመመለሳቸው በፊት ሀይቁ ዳር አረፍ ብለው የዱሯቸዉን ማውጋት ጀመሩ።
አረፍ ብለዉ ትንሽ እንደቆዩ  “ፍቅሬ! ጉልት ሰፈርን ታሰታውሰዋለህ?” ብላ ጠየቀችዉ ወ/ሮ ውድነሽ።   


“እሱማ እንዴት ይረሳል የኔ ፍቅር። ለዛሬዉ ማንነታችን መሰረቱ እሱ አይደል?” አላት በፈገግታ በተሞላ ፊት አይን አይኗን እያየ።
“እሰኪ ከዚያ የማትረሳዉን ነገር ንገረኝ!” አለችዉ የጉንጩን ጺም እየደባበሰችና አይኑን በቆረጣ እያየች እያየች።
“እ…እዛማ የሚፈራረቅብን ፀሃይና ዝናቡ፣ እቃ አልሸጥ ሲለን ሌላ እቃ ማምጣት ሲያቅተንና በጣም ስንቸገር፣…ከሁሉም በላይ የማልረሳዉ ደግሞ ከንግድ ቢሮ ነዉ የመጣነዉ ያሉ ግለሰቦች የንግድ ፈቃድ ሳይኖራችሁ መስራት አትችሉም ብለዉ መደባችን ፈራርሶ ከቦታችን ተፈናቅለን የተንገላታነዉ ነዉ” አላት።
“ኡ…ያን ጊዜማ አታንሳዉ!” አለችዉ ወ/ሮ ውድነሽ እጆቹን ጥብቅ አድርጋ እየያዘችና ትኩር ብላ እየተመለከተችዉ።
“አይዞሽ ውዴ! አሁንኮ አልፏል” አላት ዘና ባለ መንፈስ።
ቀጠል አደረገችና “ያኔ እኮ እኔ ተስፋ ቆርጬ በህይወቴ ወደኋላ የተመለሰኩበት ጊዜ ነበር” አለችው አዘኔታ በተሞላበት ድምጸት።
ወደራሱ እቅፍ እያደረገ “አዎ! ግን ያው የተለያዩ አካላት…” ሲል ሳታሰጨርሰዉ ቀበል ብላ፤
“እሱማ ነዉ።  በሴቶች ዙሪያ የሚሰሩ የተለያዩ አካላት ተቀናጅተዉ የመስሪያ ቦታችን ከበፊቱ በተሻለ መልኩ መጠለያም እንዲሰራለት፣ ለመንቀሳቀሻ ብድር እንዲመቻችልን እንዲሁም የንግድ ስራችንን እንዴት መስራትና ውጤታማ መሆን እንደምንችል ስልጠና እንድናገኝ ድጋፍ ካደረጉልን በኋላ እኮ ነዉ ወደራሴ ተመልሼ እንደገና በወኔ መንቀሳቀስ የጀመርኩት” አለችዉ።
“ከዚያ በኋላ እኮ በቃ እንደ ጥይት ተተኮስሽ” አላት ፈገግ እያለ።
“ታዲያስ! ከዚያማ ብርታት አግኝቼ ወደኋላ ላልመለስና በህይወቴ ውደፊት ብቻ ለመጓዘዝ አመረርኩኝ” ብላ እንደ መቀለድ አለችና ሳም አደረገችዉ።
ወዲያው ዞር ብሎ ተመለከተና፤ “ጨለማ እየመጣ ነዉ፤ ሰው ሁሉ ሄዶ ጭር ብሏል። እንነሳ” ብሏት እነሱም ወደ ቤታቸዉ ጉዞ ቀጠሉ። በመንገድ ላይ እሷ በግራ እጇ እሱ ደግሞ በቀኝ እጁ አንዱ የሌላኛው ወገብ ላይ በማሳረፍ ተቃቅፈዉ ነበር የሚጓዙት። ወደ ቤታቸዉ አቅራቢያ ሲደርሱ ወ/ሮ ውድነሸ ድንገት “ያዝ!” ብላ ክራንቿን ለአቶ ወርቅነህ ሰጠችው። “እንዴ ኧረ እንዳትወድቂ!” ብሎ ጮኸባት። “አይዞህ አታስብ ሌላ ምረኩዝ አለኝ። የጉልት ንግዴ በተቃወሰበት ጊዜ እንድጠነክር በማበረታታት፣ የገበያ አማራጮችን በማፈላለግ፣ የተሻለ ገቢ እንድናገኝ እና ከጉልት ወደ መደበኛ ሱቅ በመሸጋገር የንግድ ስራችን እዚህ ደረጃ እንዲደርሰ ከጎኔ ሆኖ ያበረታታኝና መቻሌን ይመሰክርልኝ የነበረ ምረኩዝ አለኝ።” አለችዉ ጭንቅላቷን በራስ መተማመን መንፈስ ወደላይ እና ወደታች እያንቀሳቀሰች።
“ምን እያልሸሀ ነዉ? ማንን ነዉ?” ብሎ ጠየቃት በአግራሞት መንፈስ እያያት።
ሳቅ እያለች በአመልካች ጣቷ ወደሱ ጠቆመች። እሱም እየሳቀ ወደራሱ አሰጠግቶ እቅፍ አደረጋት እና “ ይህንን እኮ በማድረጌ አንቺ ብቻ ሳትሆኚ እኔም ነኝ የተጠቀምኩት” አላት።
“እሱስ ልክ ነህ። መቼም ሁሉም ወንዶች እንዲህ የሚያስቡበት ጊዜ መምጣቱ አይርም” አለችዉ።
ሁለታቸዉም ተያይተዉ ተሳሳቁ። በወ/ሮ ውድነሽ በዚህ ትዝታ ውስጥ እያለች፤
“እትዬ!” የሚል ድምጽ አባነናት።
“ወይ” አለች በሃሳብ በነጎደችበት ሰረገላ ወደገሃዱ ዓለም እየተመለሰች።
ሰራተኛዋ ነበረች ምሳ እያቀራረበች የተጣራችው።
ወ/ሮ ውድነሽ በጣም ጠንካራ፣ በተስፋ የተሞላች እና ፈተና እንኳን ሲገጥማት ከጨለማ ዛሬ በስተጀርባ ብርሃን የሆነ ነገ እንዳለ የምታስብ ናት። በችግር ውስጥ ሆና ጥቃቅን መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ባገኘችው ቀዳዳ ሾልካ በመውጣት በህይወት መንገድ ላይ ጉዞዋን የምትቀጥል ሴት ናት። እንኳንስ ሴትነት አካል ጉዳተኝነት ለስኬት እንቅፋት ያልሆነባት ብርቱ የሆነች ሴት ናት። በመሆኑም የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን ያከፋፍሉበት ከነበረዉ ሱቅ በማሻሻል ያለቀላቸዉ የቆዳ ምርቶችን ለአገልግሎት ዝግጁ በማድረግ ‘በኢትዮጵያ የተሰራ’ የሚል ጽሁፍ እያተሙበት ወደ ውጭ መላክ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ምርቶቻቸዉ የበረካታ አገራት ገበያን ሰብረዉ መግባት የቻሉ ናችው። ድርጅታቸውን እሷ በስራ አስኪያጅነት ባለቤቷ ደግሞ በምክትል ስራ አስኪያጅነት ይመሩታል። አሁን ግን እሷ ሁለተኛ ልጃቸውን እርጉዝ በመሆኗ ወልዳ እስክትነሳ ባለቤቷ እሷን ተክቶ ድርጅቱን ይመራል።
ዛሬ ላይ ወ/ሮ ውድነሽ ህይወቷ ተቀይሯል። እንደዚህ አይነት ኑሮ እኖራለሁ ብላ አስባም አታውቅም። ስታስበዉ ለራሷም በጣም ትገረማለች። እሷ የሚገጥማትን ፈተናና ጫና በማለፍ ለበለጠ ውጤት መትጋት ላይ ነበር ሁል ጊዜም ትኩረቷ። ጥረቷም ፍሬ አፍርቶ አሁን ላይ ከራሷና ከቤተሰቧ አልፋ በድርጅታቸዉ ውስጥ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ችላለች።ሴቶች ሁሉ እንደሷ ጠነክረው በመስራት ከራሳቸውና ከቤተሰባቸዉ አልፈዉ ለሃገራቸው እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አጥብቃ ትሻለች። በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በቀለም እና በጾታ ሳትለያይ የሰውን ልጅ ሁሉ በምትችለዉ አቅም መርዳት ትፈልጋለች። በርካቶችንም ባገኘችው አጋጣሚ በገንዘብና በሃሳብ በመደገፍ በህይወታቸዉ አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲጓዙ ምክንያት ሆናላቸዋለች። ለዚህ ስኬቷ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተደረገላትን ድጋፍ እንደ ምክንያት ብትጠቅሰውም የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማህበር ሚና ግን የጎላ እንደሆነ ትገልጻለች ወ/ሮ ውድነሽ። በዋናነትም በማደራጀት፣ ስልጠና በመስጠት፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ እና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸዉ በማድረግ ለርካታ ሴቶች ለውጤት መብቃት ማህበሩ የተጫወተዉ ሚና አሌ የማይባል መሆኑን በመጥቀስ ሁሌም ታመሰግናለች። ኧረ እንዲያዉም አንዳንዴ የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማህበርን ‘የህይወት ጉዞ ማርሽ አስቀያሪ’ ትለዋለች። ብዙ ሴቶች የጥረታቸዉን ፍሬ እንዲበሉ ከጐኗቸዉ በመሆን ደግፏቸዋልና።


Published in ባህል

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለዳግማይ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁማ!
ስሙኝማ… ‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!” የዘንድሮውማ በዛና ግራ አጋባን፡፡ እኔ የምለው…እንዴት ነው እዚህ አገር ነገሩ ሁሉ መላ ቅጡ እንዲህ የጠፋው!
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
እኔ የምለው… የማይጨምር ምንም ነገር ላይኖር ነው!…የእንትናዬ ንጭንጭ ጨምሯል፣ የእንትና አረቄ ግልበጣ ጨምሯል፣ የአለቆች “በብጣሽ ወረቀት እንዳላባርርህ!” ጨምሯል፣ የቦሶች “እኛ ባንሆን ጠኔ ይገድልህ ነበር…” አይነት ነገር ጨምሯል፣ ከእኛ ‘ከትንሾቹ’ እስከ እነሱ ‘ትልልቆቹ’ እብሪት ጨምሯል፣ የኮንዶሚኒየም ዋጋ ጨምሯል…ያልጨመረን ነገር መዘርዘሩ ሳይቀል አይቀርም፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ ጨምራ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
ይቺን አሪፍ ቀልድ ስሙኝማ…የዶሮ እርባታ ነው፡፡ እናማ… ሌላ ቦታ የተመታ ሙሉ ለሙሉ ነጭ የእግር ኳስ ግቢው ውስጥ ያርፋል፡፡
ይሄን ጊዜ አንድ አውራ ዶሮ በጩኸት ሴት ዶሮዎችን ይሰበስብና ምን ቢላቸው ጥሩ ነው… “እኔ አቤቱታ እያቀረብኩ አይደለሁም፡፡ ግን በሌሎች የዶሮ እርባታዎች የሚጥሉት ዕንቁላል ምን እንደሚያካክል ራሳችሁ ተመልከቱ…” ብሎ እርፍ፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
ስሙኝማ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ከጊዜ ጋርና ወደድንም ጠላንም ከሚመጡ የአኗኗር ለውጦች ጋር የሆኑ ነገሮች መለወጥ ያለብን አይመስላችሁም! ቢያንስ፣ ቢያንስ የማንም መጫወቻ ከመሆን እንተርፋለና! እንደ ኮንዶሚኒየም አይነት አኗኗር እየተስፋፋ ሲሄድ… አለ አይደል… የተለመደው ዶሮ መበለት፣ በግ ‘ሸክ ማድረግ፣’ አገር ምድሩን በወይራና በኢራን ዕጣን መሙላት… ምናምን አስቸጋሪ ስለሚሆኑ ባንወድም ልንለውጣቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
እንደኛዋ ጦቢያ… አለ አይደል… በሁሉም ነገር ‘እንደ ልብ’ የሚኮንባቸው አገሮች ምን ያህል እንደሆኑ ይጣራልንማ! ምን ላድርግ… ‘ማነካካት’ ለምዶብን የለ!… ‘መነካካቱ’ ለ“እነሆ በረከት” ነገርዬ ቢሆን እኮ አሪፍ ነው፡፡ ሰውየው…
ሳናረጅ፣ ሳናፈጅ ልጅነት እያለን
መቅረታችን ነው ወይ እንዲህ ተነካክተን፣
አለ አሉ፡፡ ሳታረጁ፣ ሳታፈጁ እንዲሁ ‘ተነካክታችሁ’ አትቅሩማ!
እናላችሁ…ነገረ ሥራችን ሁሉ እየጠፋብን ነው፡፡ ለሰሞኑ የበዓል ዋዜማ የዋጋ መናር (ለአብዛኛዎቹ ነገሮች) ምንም ምክንያት የለውም። ግን መላዋ በጠፋ አገር ‘ምክንያት’ የሚባለውም ነገር ከመዝገበ ቃላት የተፋቀ ነው የሚመስለው፡፡ ሲጮህ… አይደለም ጐረቤት ሊሰማ፣ “ምነው ይሄ በግ እንዳይጮህ ማዕቀብ ተጥሎበታል እንዴ!” የሚያሰኘው ‘በግ ተብዬ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ብር! በሁለት ሺህ ስምንት መቶ ብር እኮ ለስንት ሳምንት በ‘ባላንስድ ዳየት’ ሰውነትን እፎይ ማሰኘት ይቻላል፡፡
እናላችሁ…ምንም እንኳን እንደ ትንሳኤ አይነቱ ባብዛኛው ከምግብ ጋር የተያያዘ በዓል ቢሆንም…በበዓላት ላይ የሥጋን ነገር ቀነስ አድርገን እየነዳ የመጣውን በግና ፍየል እንደገና እየነዳ እንዲመለስ ማድረግ እስካልቻልን አስቸጋሪ ነው፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!” በነገራችን ላይ…ወይ ጥሩ ነገር አይግባህ ብሎኝ እንደሆነ አላውቅም…በዘንድሮ ትንሳኤ በዓል በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የቀረቡ ‘ልዩ ፕሮግራሞች’ የጠበቅሁትን ያህል አላገኘሁትም። ምን ይደረግ “አይጣምህ…” ያለኝ ዕድለ…በዓል አልፎ በዓል ሲመጣ ‘ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ’ ሲሆን… አለ አይደል…ትንሽ ይደብራል፡፡
እኔ የምለው…‘ክሬቲቪቲ’ ምን ውሀ በላው! ዘንድሮ ‘ለኩረጃ’ ስንት የሚያመች ነገር ባለበት ያው የተለመደው “ምን ገጠመኝ አለዎት?” አይነት ነገር…አለ አይደል…ይሰለቻል፡፡ እናላችሁ…የልዩ ፕሮግራም አዘጋጆች አዳዲስ ፈጠራ ይዛችሁ ኑልንማ! ‘ስፖንሰር እንዲህ በሽ፣ በሽ በሆነበት ዘመን የፕሮግራም ጥራት ላይ አለማተኮርም ቀሺም ነገር ይሆናል፡፡
ሀሳብ አለን…ሽልማቶቹ ሁልጊዜ በጎችና የውሀ ማጣሪያዎች ምናምን ብቻ ከሚሆኑ…አለ አይደል… ለምሳሌ… “የአራት ዓመት የዲ.ኤስ.ቲቪ የደንበኝነት ክፍያ…”፣ “በአትክልት ተራ የሦስት ዓመት ሙሉ የሽንኩርት፣ የቃሪያና የቲማቲም ወጪ…”፣ “በእንትን ፎር ስታር ሆቴል ለዘጠኝ ወር ለሁለት ሰው ሙሉ የምግብና የአልጋ አገልግሎት…”  “የሁለት ዓመት የመብራት፣ የውሀና የስልክ ክፍያ…” ምናምን የሚባሉ ሽልማቶች ይካተቱልንማ! (ብቻ… የሚቀጥለው በዓል ይድረስ እንጂ የበዓል በጀቴን በኤፍ.ኤም. ሽልማት ካላሟላሁማ!)
ስሙኝማ… ቢራን የማይጠጣ ሰው እንኳን ዘንድሮ ቢራ ቢጠጣ አይገርምም፡፡ አሀ…የምር እኮ በማስታወቂያና በስፖንሰርሺፕ ‘ቢር ዋር’ ምናምን አይነት ነገር ያለ ነው የሚመስለኝ፡፡ ሀሳብ አለን… ቢራዎች… “ምርጥ ቢራ ጠርሙሱ ሁለት ብር ከሽልንግ…” ምናምን የሚል ውድድር ውስጥ ይግቡልንማ!
እናላችሁ… የሚቀጥለው ለአቅመ ስፖንሰርሺፕ የሚያበቃ በዓል ይቃረብ እንጂ…የሆነ “እንደ ጥላሁን መዝፈን እችላለሁ…” ምናምን ብዬ ለሞራሌ ወይ የሺህ ብር በግ፣ ወይ 42 ኢንች ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን የማገኝበትን ዘዴ ለመቀየስ እየሞከርኩ መሆኑን አሳውቃለሁ፡፡ አይደለም በሥራ ላይ ያሉት ኤፍ ኤሞች… “ወደፊት ሊኖሩ ይችላሉ…” የምላቸው ኤፍ፡ኤሞች አይቀሩኝም፡፡ (ሰሞኑን ጠላ አበዛሁ እንዴ! ጠላ እየተጎነጨሁ  (ስርዝ የራሴ) ኮምፒዩተር ላይ እየተየብኩ መሆኑን ሳሳውቅ ሁሉ ሰው እውነቱን እንዲያወጣ በማበረታታት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እንትና… ቅዳሜ ዕለት ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ከምናምን የደወልክልኝ ምን ‘እየተጎነጨህ’ ነበር?)
አንዱ ለጓደኛው ምን ይለዋል መሰላችሁ… “የዶሮዎች ነገር ሁልጊዜ ይገርመኛል…” ይላል። ጓደኝዬውም… “ለምንድነው የሚገርምህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየው ምን አለ መሰላችሁ… “ገና ሳይፈጠሩ የሚበሉ እንሰሳት ቢኖሩ ዶሮዎች ናቸው፡፡” እኛማ… አለ አይደል… ዘንድሮ ዶሮዎቹ ‘ተፈጥረውም፣ ሳይፈጠሩም’ ኪሳችንን የዩክሬይን ጦር ሜዳ እያስመሰሉብን ነው የተቸገርነው፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
እናላችሁ…የምር ራሳችንን መለስ አድርገን ማየት ያለብን ጊዜ ነው፡፡ “መቼም የፈለገው ይምጣ እንጂ በዓልን በባዶ ቤት አላሳልፍም…” እያልን ፈራንካችን በጠራራ ጸሀይ ‘በሱናሚ’ መወሰድ የለበትም፡፡ (‘ሱናሚ’ ያልኩት ለማጋነን እንጂ… የእኛን ገንዘብማ ቆስጣ እንኳን የማታወዛውዝ ነፋስ ይዛው እንደምትሄድ ‘ጠፍቶኝ’ አይደለም፡፡)
እናላችሁ…ዋጋ ጭማሪዎች… አለ አይደል… ምክንያታዊ ሲሆኑ… “እነሱም ምን ያድርጉ…” እንላለን፡፡ ኮሚክ እኮ ነው… ቀደም ባሉት ጊዜያት በዋዜማው… “መሸት ሲል ይቀንሳል…” ይባል እንዳልነበር ዘንድሮ እየጨለመ ሲሄድ ጭራሹኑ እየባሰበት ይሂድ!  
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
ዛሬ ተበልቶ ነገ ሆድ ባዶ ለሚሆነው ነገር… አለ አይደል… የአበዳሪ ሲሳይ መሆንም አሪፍ አይደለም። የብድር ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…
እሱዬው እሳቸው ዘንድ ይሄድና… “ጌታየ፣ እ… እ…ምን መሰለዎት…”  ምናምን እያለ ሲንተባተብ እሳቸው… “ምን ሆነህ ነው፣ ለምን በደንብ አትናገርም?” ይሉታል፡፡ እሱም፣
“ምን መሰለዎት፣ እንዲሰጡኝ…እንዲሰጡኝ…” ሲል ያቋርጡትና…
“ውሰዳት፣ ፈቅጄልሀለሁ፡፡ ውሰዳት… እንደውም የትራንስፖርቱን እኔ እከፍላለሁ…” ይሉታል፡፡ እሱም ግራ ይገባውና… “ጌታዬ አልገባኝም፣ ውሰዳት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?” ይላል፡፡ እሳቸውም… “ልጅህን ለሚስትነት ስጠኝ፣ ላግባት አይደል እንዴ ያልከኝ…” ይሉታል፡፡ እሱም…
“ኧረ አይደለም ጌታዬ፣ እኔ እንዲሰጡኝ ማለት…እንዲያ…መቶ ብር እንዲያበድሩኝ ልጠይቅዎት ፈልጌ ነው…” ይላል፡፡ እሳቸው ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“መቶ ብር! መቶ ብር አበድረኝ ነው ያልከው? የት አውቅህና ነው መቶ ብር የማበድርህ?” ብለውት እርፍ!
አንዳንድ ገና ‘ቤት ውስጥ’ ያላችሁ እንትናዬዎች… አለ አይደል… ‘ፋዘር’ ከመቶ ብርና ከእናንተ ለየትኛችሁ ‘እንደሚንገበገቡ’ አጣሩማ፡፡
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
ሰውየው ምን የመሰለ የዶሮ ጥብስ ይቀርብለታል፡፡ እናላችሁ ምን ይላል…
“ይቺን ዶሮ እንኳን አልበላም፡፡”
“ለምንድነው የማትበላው! ምን ጎደላት?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
“በመፈልፈያ ማሸን የተፈለፈለች ነች፣” ይላል፡፡
“በመፈልፈያ ማሽን መፈልፈሏን በምን አወቅህ?” ይሉታል፡፡ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እናት የፈለፈለቻት ብትሆን ኖሮ ሥጋዋ ይሄን ያህል አይጠነክርማ!” ብሎ እርፍ፡፡ (እንትና… ያቺ “ምንችክ ያለች ነች…” የምትላት እንትናዬ… በእናት ‘ብሬስት ሚልክ’ ማደግ አለማደጓን አጣራማ!)
‘ቺክን’ እንኳን በአቅሟ “ሦስት መቶ ሀምሳ ብር!”
መልካም የዳግማይ ትንሳኤ የሳምንት መጨረሻ ይሁንላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Monday, 20 April 2015 15:37

የፀሐፍት ጥግ (ስለ ሞት)

ሞት ትልቁ የሰው ልጅ በረከት ሳይሆን አይቀርም፡፡
ሶቅራጠስ
ሞት አንድ ራቅ ያለ የውሃ ዳርቻ ላይ ማረፍ ነው፡፡
ጆን ድራይድን
(እንግሊዛዊ ገጣሚ)
ሰው ሲሞት ከመፅሃፍ ውስጥ አንድ ምዕራፍ ተገንጥሎ አይደለም የሚወጣው፤ ወደተሻለ ቋንቋ ነው የሚተረጎመው፡፡
ጆን ዶኔ
(እንግሊዛዊ ገጣሚ)
ሞት ሁሌም ስጋን የሚከተል ጥላ ነው፡፡
የእንግሊዛውያን ምሳሌያዊ አባባል
ሞት ልብህን አያስደነግጠውም፤ ሁልጊዜም ለመሄድ ዝግጁ ነውና፡፡
ዣን ደ ላ ፎንቴን
(ፈረንሳዊ ገጣሚ)
ብዙ ሰዎች በ25 ዓመታቸው ቢሞቱም እስከ 75 ዓመታቸው አይቀበሩም፡፡
ቤንጃሚን ፍራንክሊን
(አሜሪካዊ ፖለቲከኛ፣ ሳይንቲስትና ፈላስፋ)
ሞት ብልህ ሰውን መክፈል የሚገባን ዕዳ መሆኑን እወቁ፡፡
ዩሪፒዴስ
(ግሪካዊ ገጣሚ)
መሞትን አልፈራም፤ ሲከሰት መገኘት ብቻ ነው የማልፈልገው፡፡
ውዲ አለን
(አሜሪካዊ ዳይሬክተር፣ ተዋናይና ኮሜዲያን)
እንደመወለድ ሁሉ መሞትም ተፈጥሮአዊ ነው፡፡
ፍራንሲስ ቤከን
(እንግሊዛዊ ፖለቲከኛና ፈላስፋ)
አንድ ሰው ኮርቶ መኖር ሳይችል ሲቀር ኮርቶ መሞት አለበት፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
(ጀርመናዊ ፈላስፋና ፀሐፊ)
መቼ እንደሚሞት የማያውቅ ሰው፣ እንዴት እንደሚኖር አያውቅም፡፡
ጆን ሩስኪን
(እንግሊዛዊ የጥበብ ሃያሲ)

Published in ጥበብ

በደቡብ አፍሪካ፣ በየመን፣ በጣሊያን
        ከምስራቅና ከምዕራብ አቅጣጫዎች የምንሰማው መረጃና ዘገባ፣ ከደቡብም ከሰሜንም የምናየው የፎቶና የቪዲዮ መረጃ፣ የግርግርና የትርምስ ወሬ ሆኗል። ቀደም ሲል በሳዑዲ አረቢያና በደቡብ ሱዳን፣ ዘንድሮ ደግሞ በተለይ ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ፣ በየመን፣ እንዲሁም ከሊቢያ ወደ ጣሊያን በሚያሻግረው የሜዲትራኒያን ባሕር ላይ የተከሰቱ ቀውሶችን ተመልክታችኋል። በደቡብ አፍሪካ ማክሰኞ እለት በተቀሰቀሰው የጅምላ ዘረኛ ጥቃት፣ ኢትዮጵያዊያን ሰለባ ሆነዋል። የጅምላ ጥቃቱ፤ በአስር ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ፣ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ ወደ 3 ሚሊዮን ስደተኞችን ለአደጋ አጋልጧል። በዚሁ ሳምንት፣ በጦርነት በታመሰችው ሊቢያ በኩል አስር ሺ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ፣ አንድ ጀልባ ተገልብጣ ከአራት መቶ በላይ ስደተኞች ሞተዋል። ይህም ብቻ አይደለም። የጎሳ ግጭትና ሃይማኖታዊ ጦርነት ባመሳቀላት የመን ውስጥ የሚገኙ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን፣ መግቢያ መውጪያ አጥተዋል።
እንደ ድሮ ቢሆን፣ በሌሎች አገራት የሚፈጠሩ ቀውሶችና ግጭቶች፣ በቀጥታ ሕይወታችንን የመንካት ቅርበት ይኖራቸዋል ብለን ስለማንገምት ያን ያህልም ባላስጨነቁን ነበር። በአፍሪካ የሰሜንና የደቡብ ጠረፎች፣ በአረብና በአውሮፓ አገራት ድንበሮች ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች፣ ከሕይወታችን ጋር የቅርብ ግንኙነት ይኖራቸዋል ብለን ካላሰብን ለምን ያስጨንቀናል? በዚያ ላይ፣ እንደ ድሮ ቢሆን፣ ስለ ቀውሶቹ በዝርዝር የምናውቅበት ሰፊ እድል ባላገኘን! አንድ ደቂቃ ከማትሞላ የዜና ቁራጭና ከተባራሪ ወሬ ያለፈ መረጃ አናገኝም ነበር።
ዛሬ ግን እንደድሮ አይደለም። እስከተጠቀምንበት ድረስ፣ የመረጃ ባዕድ ወይም የአፈና ሰለባ የማንሆንበት እድል ተፈጥሯል - የሳተላይት ዲሽና ኢንተርኔት በመሳሰሉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶች። የቢዝነስ ድርጅቶች ደግሞ፣ ቴክኖሎጂውን ወደ ምርትና ወደ ንግድ አሳድገው፣ ለአለም አዳርሰውታል። የየትኛውም ሃይማኖትና እምነት ተከታይ አልያም የየትኛውም አገርና ብሔር ብሔረሰብ ተወላጅ ብንሆን ለውጥ የለውም። አፕል እና ሳምሰንግ የመሳሰሉ የሞባይል ቀፎ አምራች ኩባንያዎች፤ እንዲሁም ጉግል፣ ፌስቡክ እና ዩቱብ የመሳሰሉ የቢዝነስ ኩባንያዎች፤ ቴክኖሎጂው እጃችን ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል። ቴክኖሎጂውን የመጠቀም ምርጫና ብቃት፣ የግል ምርጫችን እንዲሆን ሰፊ እድል ከፍተውልናል። አይገርምም? በጥቂት ዓመታት ውስጥ የመጣ ተዓምረኛ ለውጥ ነው። ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
አንደኛ፤ በጭፍን እምነት፣ በጭፍን “ባህል” እና በጭፍን ፕሮፖጋንዳ ምትክ፤ ለአእምሮ ክብር የሚሰጥ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የመረጃ ነፃነት ሲስፋፋ.... ሁለተኛ፤ በመንግስት ገናና የኢኮኖሚ ቁጥጥር፣ በድጎማና በጥገኝነት ፋንታ፤ ለብልፅግና ክብር የሚሰጥ ቢዝነስ፣ ንግድና ትርፋማነት ሲያድግ... ሦስተኛ፤ በጅምላ ፍረጃ፣ በቡድናዊነትና በብሔረተኝነት (በዘረኝነት) ምትክ የእያንዳንዱ ሰው ማንነት እንደየግለሰቡ ብቃት፣ ባህርይና ሰብእና የመመዘን ፍትሃዊነትና የእኔነት ክብር ሲስፋፋ፣ የሰው ልጅ ድንቅ ተዓምሮችን ይሰራል። እነዚህ ሦስቱ ነጥቦች (ሳይንስ፣ ካፒታሊዝም እና የግል ማንነት) መሰረታዊዎቹ የስልጣኔ እሴቶች መሆናቸውን ልብ በሉ።
ለነገሩ፤ በየአቅጣጫው የምናየው የኢትዮጵያዊያን ስደትም፤ ከእነዚሁ ሦስት የስልጣኔ እሴቶች ጋር የተቆራኘ ነው። የዚህን ወይም የዚያን ሃይማኖት እምነትንና ቀኖና ፈልገው አይደለም የሚሰደዱት። የአገር ወይም የብሔር ብሔረሰብ ጥንታዊ ባህልን፣ ቋንቋንና የጅምላ ማንነትን ፍለጋ አይደለም የሚሰደዱት። ለመንግስት ቁጥጥር ለመገዛት፣ አልያም የመንግስት ጥገኛ ሆነው ድጎማ ለመቀበል ጓጉተው፣ ወይም የሃብት ልዩነት የሌለበት አለም ናፍቋቸው አይደለም የሚሰደዱት። በተቃራኒው፤ ለሃይማኖትና ለእምነት ልዩነት ቦታ ባለመስጠት ነው የሚሰደዱት። የጥንታዊ ባህልና የተወላጅነት ልዩነቶችን ወደ ጎን በማለት ነው የሚሰደዱት። ለመንግስት ድጎማና ለሃብት ክፍፍል ቦታ ባለመስጠትም ነው የሚሰደዱት።
ይልቅስ፣ በሃይማኖት ላይ ሳይሆን በአእምሯቸው ላይ ተማምነው፣ በተወላጅነት ላይ ሳይሆን በግል ብቃታቸው ላይ ተማምነው፣ በመንግስት ድጎማ ሳይሆን በራሳቸው ጥረት ሃብት አፍርተው ሕይወታቸውን ለማሻሻል ነው የሚሰደዱት - የመበልፀግ መልካም ምኞታቸውን እውን ለማድረግ። በአጭሩ፤ ሦስቱ የስልጣኔ እሴቶችን የተላበሱ ናቸው። ነገር ግን፣ የስልጣኔ ፊታውራሪዎች ናቸው ማለት አይደለም። በጭራሽ። እንደአብዛኛው ሰው ሁሉ፣ ስደተኞችም በአብዛኛው ከስልጣኔ እሴቶች ጋር፣ ፀረ ስልጣኔ አዝማሚያዎችንም አዋህደው የያዙ ናቸው። እንዴት በሉ።
ዘመኑ የስልጣኔ ዘመን አይደለም። ከስልጣኔ እሴቶች በተቃራኒ፣ ሦስት የስልጣኔ እንቅፋቶች በዓለም ዙሪያ ያንሰራሩ የመጡበት ዘመን ላይ ነው የምንገኘው - የጭፍን እምነት ስብከትን የሚያራግብ የሃይማኖት አክራሪነት፣ የሃብት ክፍፍል ዲስኩር የሚዘወተርበት የመንግስት ገናናነት፣ ጥንታዊ ባህልን በማምለክ የሚለፈፍበት ዘረኝነት፣ እንደ አሸን ሲፈሉ የምናየው ለምን ሆነና! በእነዚህ ሦስት ፀረስልጣኔ አቅጣጮች ምክንያት የሚከሰቱ ቀውሶችን ነው በአለም ዙሪያ የምናየው - (የአውሮፓ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ፣ የመካከለኛው ምስራቅ ሃይማኖታዊ ሽብርና ጦርነት፣ የአፍሪካ የዘረኝነትና የጎሳ ትርምስ)። ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም በየቦታው ሰለባ እየሆኑ ነው።  
ለነገሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ቢመጣም፣ አምናም ተመሳሳይ ነገሮችን እንዳየን የምንረሳው አይመስለኝም። “የአገርን ሃብት ትቀራመታላችሁ፤ የስራ እድልን ታጣብባላችሁ፤ ሃይማኖትን የሚቃረን ባህርይ ታስፋፋላችሁ” በሚል፣ ከመቶ ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከሳዑዲ ዓረቢያ ሲባረሩ አይተናል። በጥንታዊ የባህል ልዩነትና በጎሳ ተወላጅነት የተቧደኑ የደቡብ ሱዳን ታጣቂ ጎራዎች ከፈጠሩት ጦርነት ጋር በተያያዘም፣ “መጤዎች የአገራችንን ወይም የጎሳችንን ሃብት ይመዘብራሉ” በሚል በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ለአደጋ መጋለጣቸውን እናስታውሳለን። ዘንድሮም ተመሳሳይ ነው።
ከላይ እስከ ታች በጦርነት እየነደደች ባለችው የመን ውስጥ፤ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ተስፋቸው ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡት። እንደ ሌላው ዓለም በኢኮኖሚ የተቃወሰችው የመን፣ አንደኛውን ለይቶላት በጎሳ ግጭትና እና በሃይማኖታዊ ጦርነት ስትታመስ ይሄውና ዓመት ሊሆናት ነው። እንዲያም ሆኖ፣ በዓመት ውስጥ ከ60ሺ በላይ ኢትዮጵያዊያን ባህር አቋርጠው የመን ገብተዋል። የአገሪቱ ጦርነት ከመርገብ ይልቅ እየተባባሰ ከመምጣቱም በተጨማሪ፣ ውስጥ ውስጡን ሺዓ እና ሱኒ በሚል ሲፎካከሩ የቆዩት የኢራንና የሳዑዲ ዓረቢያ ጎራዎች አሁን በይፋ ገብተውበታል። ኢራን የጦር መርከቦችን ስታሰማራ፣ ሳዑዲ በበኩሏ በጦር አውሮፕላኖች የድብደባ ዘመቻ ስታካሂድ ሰንብታለች። እንዲያም ሆኖ፣ የዩኤን መረጃ እንደሚያመለክተው በመጋቢት ወር ብቻ ከ3ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመን ገብተዋል። ያሳዝናል፤ ግራ ያጋባል። ግን አዲስ ክስተት ካለመሆኑም በተጨማሪ፤ እልባትና መፍትሄ የሚገኝለት አይመስልም።
በደቡብ አፍሪካ፣ የኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ሕይወት የቀጠፈው የሰሞኑ ዘረኛ ጥቃትም፣ ድንገተኛ አዲስ ክስተት አይደለም። ለአመታት ሲንተከተኩ በዘለቁ ፀረ ስደተኛ ስሜቶች፣ በተለይ ደግሞ ከጥቅምት ወር ጀምሮ በየአካባቢው ሲቆሰቆሱ በቆዩ ጥቃቶች ምክንያት የተጨነቁ በርካታ የረድኤት ድርጅቶች፣ “ይሄ ነገር አደገኛ ነው” እያሉ ለማስጠንቀቅና ለመምከር ሲሞክሩ ከርመዋል። አንዳንዶቹም፣ “የተወሰኑ ስደተኞች ወንጀል ስለፈፀሙ፣ ስደተኞችን በጅምላ አትጥሉ። እያንዳንዱን ስደተኛ በግል ተግባሩ እንዳኘው። በርካታ ስደተኞች በራሳቸው የግል ጥረት ሃብት በማፍራትና ሃብት በመፍጠር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ጠቃሚ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ” በማለት መከራከሪያ ለማቅረብና ለማሳመን ተጣጥረዋል። በተጨባጭ መረጃ የተደገፈ ጥናታዊ ፊልም፣ ዘገባ እና መግለጫ በማሰራጨት የጥላቻ ስሜቶችንና የጅምላ ፍረጃን ለማርገብ ደፋ ቀና ብለዋል። ምን ያደርጋል? ብዙዎቹ ሰሚ አላገኙም። ሰሚ ያገኙትም፣ የሚያምናቸው አላገኙም። ጥረታቸውና ሙከራቸው፣ ከመነሻው ከንቱ እንደሆነ አላወቁም። ድንገት ተነስተው፤ “ስለ ተጨባጭ መረጃ፣ ስለ ሃብት ፈጠራ፣ ስለ ግል ማንነት” የሚያወሩት ነገር ውጤት አላስገኘም። ለምን ቢባል፤ አብዛኞቹ የረድኤት ድርጅቶችን ተመልከቷቸው።
ከፊሎቹ የእርዳታ ድርጅቶች፣ የምዕራባዊያንን የሳይንስና የስልጣኔ እመርታን የሚያወግዙ የሃይማኖት ሰባኪዎች ናቸው። በአንድ በኩል ጭፍን እምነትን እየሰበኩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “እባካችሁ ለተጨባጭ መረጃ ክብር በመስጠት ከጭፍን ስሜታዊነት መታቀብ ያስፈልጋል” ቢናገሩ ማን ይሰማቸዋል? ከንቱ ንግግር ነው።
ከፊሎቹ የእርዳታ ድርጅቶች ደግሞ፣ በ“ሃብት ፈጠራ” ላይ ሳይሆን በ“ሃብት ክፍፍል” ላይ የተመሰረተ ሶሻሊስታዊ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ በማንገብ የምዕራባዊያንን የካፒታሊዝም ዝንባሌ የሚያጥላሉ ናቸው።
“የሆነ የአገር ሃብት አለ። ዋናው ቁምነገር፣ ያንን ሃብት የማከፋፈል ጥያቄ ነው” ብለው ያምናሉ። ሃብት ማፍራትንና ሃብት መፍጠርን እንደቁምነገር ስለማይቆጥሩትም ነው፤ ብዙዎቹ የረድኤት ድርጅቶች ባለሃብቶችንና የቢዝነስ ድርጅቶችን ሲያወግዙ የምንሰማው። “የሆኑ ሰዎች የሚበለፅጉት፣ ሃብት ስለሚያፈሩ ሳይሆን፣ ከአገር ሃብት ውስጥ ከድርሻቸው የበለጠ ሸምጥጠው ስለሚወስዱ ነው” ብለው ያምናሉ። እንደዚህ አይነት እምነት የያዘ ሰው ስደተኞችን መጥላቱ የግድ ነው። ስደተኞችን ባየ ቁጥር፤ “የአገርን ሃብት የሚሸመጥጡ ተጨማሪ እጆች መጡብኝ፤ ድርሻዬን ይቀራመቱብኛል” ብሎ መስጋቱ አይቀርማ። እና፣ እለት በእለት “ስለ ሃብት ክፍፍል” የሚደሰኩሩ የእርዳታ ድርጅቶች፣ ድንገት ተነስተው፣ “ስደተኞች ሃብት ያፈራሉ” የሚል አንድ ጥናታዊ ፊልም ቢሰሩ ቅንጣት ለውጥ አያመጣም።
የባህል ጥበቃን የሚሰብኩ ሌሎቹ የእርዳታ ድርጅቶችም እንዲሁ፣ የምዕራባዊያንን ዝንባሌ ያወግዛሉ - በባህል ወራሪነት ወይም በባህል የለሽነት እየወነጀሉ። “የሰው ማንነት የሚወሰነው በአገሩ ወይም በብሄረሰቡ ባህል ነው” እያሉ ዘወትር የጅምላ ማንነትን የሚሰብኩት እነዚሁ የረድኤት ድርጅቶች፤ ድንገት አንድ ቀን ተነስተው “ከሌላ አገር የመጡ ስደተኞችን አትጥሉ፤ በጅምላ አትፈርጁ” የሚል ቁራጭ መግለጫ ቢያሰራጩ፣ ኢምንት ለውጥ አያመጡም።
ታዲያ፣ ቀውሱ፣ ግጭቱ፣ አደጋው በየአመቱ እየተደጋገመና እየተባባሰ መምጣቱ፣ ከዚያም አልፎ መፍትሄ አልባ መምሰሉ ይገርማል?

Published in ህብረተሰብ

ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ፡፡ ቅዳሜ ዕለት ነው፡፡ በቀጣዩ ወር የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ በተመለከተ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ከሚቀርቡ “ክርክርና ቅስቀሳ” ቢጤዎች ባሻገር እዚህም እዚያም ከሚዘጋጁ መድረኮች በአንዱ ተገኝቻለሁ፡፡ ጉዳዩን ክርክር ቢጤ ያልኩት የምርጫ ክርክር ማለት ምን ማለት እና እንዴት  እንደሆነ በቅርቡ በአፍሪካ በዴሞክራሲው ሰፈር አንቱታን ባተረፈችው ናጄሪያ የተካሄደውን ምርጫ ሲያቀብጠኝ ተከታትዬ ነው። መቼም ምኞት አይከለከል ለሃገሬም ተመኘሁት፡፡
በቅርቡ ለንባብ በበቃ አንድ ጋዜጣ ላይ የገዢው ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ፤ “ከኢሕአዴግ ጋር አይደለም ሊፎካከር አጠገቡ የመቆም አቅም ያለው ተፎካካሪ ፓርቲ የለም” ማለታቸው ይህንን ምኞቴን ከንቱ ያደርገዋል፡፡ እኔን ግርም የሚለኝ ኢሕአዴግ አጠገብ ድርሽ የሚል ተፎካካሪ ከሌለ  ምርጫ እየተባለ የሌለ የሀገርና የህዝብ ሃብት ለምን በከንቱ እንደሚባክን ነው፡፡ ስንት መስኖ፣  ስንት ት/ቤት፣  ስንት ጤና ጣቢያ በተሰራበት ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን የኮንዶሚኒየም እጣ ደርሷቸው  የሚከፍሉት በማጣት በጭንቀት ለህምም ተዳርገዋል ለተባሉት የአዲሳቤ ነዋሪዎች በድጎማ መልክ ቢከፋፈል እንኳ ትልቅ ነገር ነው፡፡
እኔን እስከሚገባኝ ምርጫ የሚካሄደው አማራጮች ሲኖሩ ነው፡፡ መቼም አንድ አይነት ዳቦ ብቻ በቀረበበት ገበታ ላይ “መርጠህ ያማረህን ብላ” አይባል ነገር፡፡ ከተባለም ማላገጥ ነው የሚሆን ነው። የኢሕአዴጉ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ባሉት ነገር ላይ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ፓርቲያቸው የሚፎካከረው ቀርቶ አጠገቡ የሚደርስ ፓርቲ እንዳይኖር በትጋት መስራቱ ለዚህ ውጤታማ አፈጻጸም አብቅቶት ይሆን? ይህን ድንቅ የዴሞክራሲ ተሞክሮውን ለሌሎች አገራት በተለይም ለእንግሊዝና አሜሪካ ቢያጋራው የአለማችን ዴሞክራሲ ምንኛ በተመነደገ ነበር!
ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስ፡፡ የተገኘሁበትን መድረክ ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የኮሚኒኬሽን ት/ቤት መሆኑን የጥሪው ካርድ ይናገራል፡፡ “በምርጫ የሚዲያ ሚና፣  የኢትዮጵያ  ተሞክሮና በቀጣዩ ምርጫ ላይ ያለው አንደምታ” ለምክክር የተመረጠው ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ የሚዲያ ባለሙያ ወይም የምርጫው አስመራጭም ተመራጭም አይደለሁም፡፡ በሌላ የትምህርት ክፍል የምማር የዩኒቨርሲቲው እጩ ተመራቂ ብቻ ነኝ፡፡ እንደተለመደው ፕሮግራሙ ዘግይቶ ተጀመረ፡፡
የክብር እንግዳው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ናቸው፡፡ ዘግይተውም ቢሆን ሳይመጡ ቀሩ፡፡ ጥናት አቅራቢዎቹ ግን ዘግይተውም ቢሆን መጥተዋል፡፡ በረፋዱ ክፍለ ጊዜ ሁለት የመወያያ ጥናቶች  ቀረቡ። አንደኛው በት/ቤቱ ዲን ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ የቀረበ ነበር፡፡ በምርጫ ወቅት የሚዲያ ሚና ምን መሆን እንዳለበት አለም አቀፍ የሙያውን  መሰረታዊ መርሆዎች በአማረ ሁኔታ የዳሰሰ አስተማሪ ጽሁፍ ነው፡፡ የEBC እና የFBC (ፋና)  አለቆች ቢኖሩ ብዬ ተመኘሁ፡፡ በድርጅት ስብሰባ ላይ እንጂ እንዲህ አይነቱ እውቀት  በሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ አዘውትረው ቢገኙማ  ተቋሞቻቸው እንዲህ ህዝብ የሚታዘባቸው ባልሆኑ ነበር ብዬ አሰብኩ። የEBC የካሜራ ባለሙያዎች ግን ነበሩ፡፡ የዶክተሩ ሃሳብ በቤቱ የተወደደና የተጨበጨበለት ሆኖ ተጠናቀቀ። “የተማረ ይግደለኝ” የሚለው የከረመ አባባላችን ከዘመኑ ጋር መታደስ ያለበት ይመስለኛል። ለአስተሳሰብም ህዳሴ ያስፈልገዋል፡፡ አሁን አሁን ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ዲግሪ ለመጫን ቀልድ ሆኗል፡፡ በዚሁም ልክ በጫነውና ባልጫነው መካከል ያለው የልዩነት መስመርም ደብዝዟል፡፡ ስለዚህ “የተማረና የሚያነብ ይግደለኝ” በሚል ቢስተካከልስ፡፡
በቤቱ አነጋጋሪ የነበረው ቀጥሎ የቀረበው ጽሁፍ ነው፡፡ አቅራቢው ደግሞ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወልዱ ይመስል ነበሩ፡፡ በአንድ ልቤ የፋናው አለቃ በመገኘታቸው ደስ አለኝ፡፡ ጽሁፉ ጥናታዊ እንደሆነ በፕሮግራሙ ላይ የተጠቀሰ ቢሆንም አቅራቢው ጥናታዊ እንዳልሆነ አስቀድመው ተናገሩ፡፡ ከዶክተሩ የተጨበጨበለት ምሁራዊ ትንተና አንጻር ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ስገምት አቅራቢው አሳዘኑኝ፡፡ የእርሳቸው ርዕሰ ጉዳይ በሀገራችን በ1997 እና በ2002 በተካሄዱት ምርጫዎች በተለይም የብሮድካስት  ሚዲያው ሚና ምን ነበር የሚል ነው። በተለይም ምርጫ 97ን ሊነካኩት መሆኑ ሲገባኝ ደስታም ቅሬታም ተፈራረቁብኝ። ኢሕአዴግም በአቶ በረከት “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ላይ እንዳመነው፣ ይህ ወቅት የሀገራችን ዲሞክራሲ ህዝብን በሙሉ ፍላጎት ያሳተፈ ነበር፡፡ ከታሪካዊ አመጣጡ ጀምሮ የገዢው ፓርቲ ፍላጎትና ርዕዮት ይጫነዋል የሚባለው የዚያኔው ሬዲዮ ፋና ደግሞ ትልቅ ሚና ነበረው። ሚናው ለዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ግንባታ ጠቀመ ወይስ ጎዳ? የሚለው ጉዳይ ግን መጤን ያለበት ይመስለኛል፡፡ እናም የዚህን አነጋጋሪ ጣቢያ እይታ ለዚያውም ከዋናው ሰውዬ ልሰማ መሆኑን ሳስብ ነው ደስ ያለኝ፡፡ ቅሬታዬ ግን አቅራቢው እንዳሉት ይህን ጉዳይ ያውም ያለምንም የተደራጀና ጥልቀት የሌለው ጥናት መነካካቱ የሚቀርበውን ነገር ከእውቀት የፀዳና ስሜታዊነት ያጠቃው እንዳይሆን አስግቶኝ ነበር። አቶ ወልዱ የሚያቀርቡት ነገር ጥናት ያልሆነበት ምክንያት ያዘጋጁት ነገር ስለጠፋባቸው ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ በተሰጣቸው ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ወዲህና ወዲያ እየተላጉም ቢሆን ለማለት የፈለጉትን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡
ሃሳባቸው ሲጠቃለል በምርጫ 97 በተለይ የብሮድካስት ሚዲያው /ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ማለታቸው ነው/ ምርጫው ህዝብ በንቃት የተሳተፈበትና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የላቀ ሚና ተጫውቷል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ በሌሎች በዴሞክራሲ በዳበሩት አገራት እንኳን ባልታየ መልኩ ምርጫው ሊከናወን መንፈቅ ሲቀረው ጀምሮ የምርጫ ክርክሩና ቅስቀሳው መጀመሩ ነው። ይሄ ደግሞ አቅራቢውን ያስቆጫቸው ይመስላል። ኢሕአዴግም ቆጭቶታል ልበል? ለዚህም ይመስለኛል የዘንድሮው ምርጫ ለመካሄድ ሁለት ወር ያልሞላው ጊዜ ሲቀረው ያውም በተቃዋሚዎች ውትወታ የተጀመረው፡፡ ከስህትት መማር ማለት እንዲህ ነው፡፡
አቅራቢው ሲሆን የነበሩ ነጻ (የግል) የህትመት ውጤቶች ከብሮድካስት ሚዲያው በተቃራኒ ቆመው እንደነበር፡፡ ይህን ኢሕዴግም ሲለው የነበረ ሲሆን አብዝቶም በመጸጸቱ እየተንገታገቱ ካሉት ጥቂት በቀር ሁሉንም የፕሬስ ውጤቶች በአንድ ፈርጆ ድምጥማጣቸውን ያጠፋ በመሆኑ የአቅራቢው ድምዳሜ ብዙም አልገረመኝም፡፡ ለእኔም ሆነ በኋላ እንደታዘብኩት ለብዙዎቹ የመድረኩ ታዳሚያን የገረመን ሰውየው የሚዲያ ባለሙያ ሆነው ያውም ለ20 አመታት የቆዩና ከዚህም ውስጥ የሚበዛውን ጊዜ በፋና ትልቁ ወንበር ላይ የተቀመጡ መሆናቸውን ሳገናዝብ ነው፡፡ ድምዳሜያቸው ስህተት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ቢያንስ ሁሉንም በአንድ ፈርጆ ከመውቀጥ መለየት እንኳን ይገባቸው ነበር፡፡ የኢሕአዴግን አቋም የማይደግፍና የእሱን የልማት ስራ አጋኖ ሳያቋርጥ የማይዘግብ (ልማታዊ ያልሆነ) ሚዲያ መኖር የለበትም የሚል አቋማቸውን ለማስተጋባትም ተከታዩን ድምዳሜ አቅርበዋል፤ “በተለይ የምርጫ 97 ውጤትን ተከትሎ በሃገሪቱ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ አገሪቱ ልትፈራርስና ወደማያባራ ግጭት ልትገባ በቋፍ ላይ ነበረች። በዚህ ቀውጢ ጊዜ አገርን ለማዳን በተደረገው ርብርብ የብሮድካስት ሚዲያው ትልቁን የማረጋጋት ሚና ተጫውቷል፡፡ የህትመት ሚዲያው ግን ከዚህ በተቃራኒው በመቆም አገሪቱን ወደማያባራ እልቂት ለመጨመር ሲሰራ ነበር፡፡” /እንደወረደ የቀረበ/በ97ቱ ምርጫ ወቅት የብሮድካስት ሚዲያ የመንግስት ቲቪና ሬዲዮ እንዲሁም ፋና ሬዲዮ ብቻ ነበሩ ልብ ይሏል፡፡ አገር አዳኞቹም እነርሱው ነበሩ። ዛሬ ከእልቂት ተርፈው እየተፍጨረጨሩ ያሉት “ሪፖርተር”ና “አዲስ አድማስ” እንኳን አልታያቸውም።
አቶ ወልዱ እንደተናገሩት፤ ከ97 ምርጫ አንጻር  በ2002 ምርጫ የነበረው የሚዲያ ሚና የተሻለ ነበር፡፡ ለዚህም መንግስት አብዛኞቹን በእርሳቸው አገላለጽ፤ “አገር ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የህትመት ተቋማትን እንዲዘጉ በማድረጉ ነው፡፡ ስለሆነም ከ97ቱ የተሻለ ህዝብ በብዛት የተሳተፈበትና ችግር ያልነበረበት ምርጫ ተካሂዷል፡፡ አቅራቢው የግል ፕሬሱ ድምጥማጡ በመጥፋቱ የተደሰቱ ይመስላሉ። በአንድ በኩል እውነት አላቸው፡፡ በገበያ ውስጥ ያለ ተቋም እንደመምራታቸው መጠን ያለተፎካካሪ የሃሳብ ገበያውን ለመጋለብና ህዝቡን ጋሪ እንደሚጎትት ፈረስ እርሳቸውና ፓርቲያቸው በሚፈልጉት መንገድ ብቻ ለመምራት ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። ግን ደግሞ 20 አመት ያውም የሚበዛውን ጊዜ በሃላፊነት በሚዲያው አለም የቆዩ እንደመሆናቸው መጠን የግሉም ይሁን ሌላው ሚዲያ እንዲያብብ መመኘት፣ ለዚህም መስራት ይጠበቅባቸው ነበር የሚል እምነት አለኝ። እውን የዴሞክራሲ መስፈን አሳስቧቸው ከሆነ ወደ በረሃ የገቡት ማለቴ ነው፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ዶ/ር አጋረደች የተባሉ ምሁርም ይህንኑ የሚያጠናክር ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ “የግል የህትመት ሚዲያው በመክሰሙ ደስ ያለዎት ይመስላሉ፡፡ ችግር አለባቸው ከተባለ ችግራቸውን በሂደት እያረሙ እንዲኖሩ ማድረጉ ለህዝብና ለዴሞክራሲ ስርአቱ ግንባታ ይበጅ የነበረ አይመስሎትም ወይ?” አሏቸው፡፡
አቶ ወልዱ አጠገባቸው የተቀመጡትንና ቀደም ብለው ወረቀት ያቀረቡትን ዶ/ር አብዲሳን አልሰሟቸውም እንጂ  ይህንን ተናግረው አቧራ ባላስነሱ ነበር፡፡ ዶ/ሩ የቀድሞውን የአሜሪካን ፕሬዝደንት ንግግር ነበር የጠቀሱት፡- “በአጣብቂኝ አማራጭ ውስጥ ገብቼ ፕሬስ አልባ መንግስት ከሚኖርና መንግስት አልባ ፕሬስ ከሚኖር ምረጥ ብባል የኋለኛውን የምመርጥ ይመስለኛል”፡፡ በርግጥ ዶ/ሩ የፕሬዚዳንቱን አባባል በአውዱ /contextually/ መረዳት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡- የሁለቱም መኖር ለአንድ አገር የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት በመስጠት፡፡ አቶ ወልዱ የሚያቀርቡትን ሲያጠናቅቁ እንደመጀመሪያው አቅራቢ ያልሞቀ ግን ደብዘዝ ያለ የአክብሮት ጭብጨባ አግኝተዋል፡፡
“ሞጋቹ” ሲሞገት
በእኒህ መሰሉ መድረኮች ላይ ስገኝ ሁሌም የሚገርመኝን ነገር በቅድሚያ ላንሳ፡፡ ብዙው የውይይት ጊዜ የሚፈጀው በጥናት አቅራቢዎቹ ነው። ያውም የሚበዙት ጥናት ያልሆኑ ጥናቶች እያቀረቡ፡፡ ምክክር እንዲህ ነው እንዴ?!
እንዲህም ሆኖ ወደ ውይይቱ ተገባ፡፡ ገና እድሉን ለመስጠት አወያዩ ሲያስቡ፣ ብዙ እጆች አየር ላይ ነበሩ፡፡ ያለማጋነን እጁን ያላወጣው ታዳሚ በቁጥር ያንስ ነበር፡፡ ሃሳብና ጥያቄዎች ከግራ ከቀኝ፣  ከግንባር ከደጀን መዥጎድጎድ ጀመሩ፡፡ አብዛኞቹ የጎረፉት ወደ አቶ ወልዱ ነበር፡፡ ካቀረቡት ሃሳብ አንጻር የሚጠበቅ ስለነበረ አልገረመኝም፡፡ ምናልባት እርሳቸው በለመደ ፍረጃቸው ጠያቂዎቹን ሁሉ ምድረ “ኒዮ ሊብራሊስቶች” ወይም “ፀረ ልማቶች” ብለው ፈርጀውን ሊሆን ይችላል፡፡ የሚቻል ቢሆንም ግን ጠቃሚ አይመስለኝም፡፡
ከምርጫው ጋር በተያያዘ ጣቢያቸው “ሞጋች” የሚባል ፕሮግራም ከፍቶ የተለያዩ ፓርቲዎችን እየጠራ የጣቢያው አወያይም ጭምር ከኢህአዴግ ጎን ተሰልፎ ጉንጭ አልፋ ክርክር እንደሚያደርግ እኔ በግሌ አውቃለሁ፡፡ ለፋናው አለቃ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል በተለይ የዚህ የሞጋች ነገር ቀልቤን ስቦታል። የኔው ቢጤ አንዱ ተማሪ ጉዳዩን እንዲህ በማለት ነበር ያነሳው፤
“ፋና ከየት እንደመጣና አላማው ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ከ24 አመታት በኋላም የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ ማለቱን አልተወውም፡፡ ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ሃሳቦች እንዲደመጡ ፍላጎት የለውም። በተለይ በዚህ ሞጋች በምትሉት ፕሮግራም አወያይ ብላችሁ ያስቀመጣችሁት ሰው ግልጽ የሆነ አምባገነንነትና ጉልበተኝነት ይታይበታል። ለኢህአዴግ መወገኑ በግልጽ ይታወቅበታል። ከሙያውም ስነምግባር በጣም የራቀ ነው፡፡ ሰውዬው ለፋና ሊመጥን ይችላል፡፡ ለሚያዳምጠው ህዝብ ግን አይመጥንም፡፡ ስርአት የለውም፡፡”
ሌላዋ ተወያይ ቀጠሉ፡-
“እኔ የማውቀውና የማስተምረው ጋዜጠኝነት ይህንን አይነቱን ኢ-ስነምግባራዊ የሆነ ድርጊት አይፈቅድም፡፡ ጣቢያችሁ ሚዲያ ሆኖ ሳለ የእናንተ ጋዜጠኛ ግን በተለይ የህትመት ሚዲያውን ሲዘልፍና ሲያብጠለጥል ነው የሚውለው፡፡ ሞጋች እያለ የሚያቀርበውም ፕሮግራም ፍጹም ስነምግባር የጎደለውና የሰውን ክብር የሚነካ ነው። የሚጋብዛቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች የራሳቸው ደጋፊና ተከታይ እንዳላቸውና እነዚህም እንደ ኢህአዴግ ደጋፊዎች ሁሉ የተከበሩ ህዝቦች መሆናቸውን ሊያውቅ ይገባል፡፡ግን ሰውዬው ምንድነው?”
የፋናው አለቃ ይህንና ሌሎችንም ጉዳዮች  በተመለከተ የቀረበባቸውን ትችት መቋቋም እየተሳናቸው ሲመጡ በግልፅ ተስተዋሉ፡፡ ምላሽ እንዲሰጡ እድል ተሰጣቸው፡፡ ምላሻቸውም በአብዛኛው የሚያበሳጭና ዙሪያ ገባውን ያላስተዋለ ነበር፡፡ በተለይ አጠገባቸው የነበሩትን ዶ/ር መዘንጋታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ “ሞጋች” በተባለው ፕሮግራማቸው ላይ የተነሱባቸውን ትችቶች ግን ሙሉ ለሙሉ ተቀብለው ለማስተካከል እንደሚጥሩ በሚያስተዛዝን ድምጸት ተናገሩ፡፡ እኝህ ሰው የድርጅቱ ዋና ሰው ናቸውና ያስተካክሉታል ብዬ ተስፋ አደረግሁ፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ፕሮግራም እጅግ ከሚበሳጩትና እንዲህ አይነት ጋዜጠኝነት በአለም ላይ አለ ወይ ስልም ከሚጠይቁት ወገኖች አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ ከዚህም በመነሳት ነው እንግዲህ ፋና በ97ቱም ሆነ ከዚያ በኋላ በተደረጉትና በቀጣዩም ምርጫ የነበረውና የሚኖረው ሚና መጤን አለበት ማለቴ፡፡
የፋናው ዋና ራስ ስህተት መሆኑን የተቀበሉትንና ይቅርታ የጠየቁበትን ጉዳይ እንዴት እንደሚያስተካክሉት ለመታዘብ እሁድ ረፋድ ላይ ሬዲዮኔን ከፈትኳት፡፡ ያአምባገንነትና ጉልበተኝነት” ይስተዋልበታል የተባለው አወያይ አየሩን እየተገፋተረም እያሸማቀቀም መጣ፡፡ ለውጥ አልታየበትም፡፡ መጨረሻውን ለማየት ማድመጤን ቀጠልኩ፡፡ ሰማያዊ ፣ አንድነትና  ኢህአዴግ ናቸው ለሙግቱ የቀረቡት፡፡ የኢራፓው ተወካይ ተጋብዘው ሳይሆን “ተጠርተው” እንደቀሩ ጋዜጠኛው ደጋግሞ ተናገረ፡፡ እመጣለሁ ብሎ መቅረት ተገቢ ባይሆንም ግን ደግሞ መብት መሆኑን ጋዜጠኛው የዘነጋው ይመስላል፡፡ ካሉበት በአስቸኳይ እንዲመጡም ጮክ ብሎ ተጣርቶ ነበር፡፡ ሳይመጡ ቀሩ እንጂ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲሀ መሃል ላይ ላይ ችግር ተፈጥሮ አየሩ ደም ደም መሽተት የጀመረው፡፡ እኔ እምለው ግን ፋና ስቱዲዮ ውስጥ ያለው የውይይት ጠረጴዛ ነው ወይስ ታንክ? የምሬን እኮ ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ ሳይሆን ታንክ ከበው የሚነጋገሩ ነው የሚመስሉት፡፡ ነገሩን አደፍርሶ የአወያዩን ቁጣ ጣሪያ ያደረሰው ደግሞ በተለይ የሰማያዊ ፓርቲው ተወካይ ሃሳብ  ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ሰው (አቶ ዮናታን) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የምክክር መድረክ ላይ ተገኝቶ ነበር፡፡ አወያዩ ለዚህ ሰው እንዲናገር እድል ይሰጠዋል ግን አያናግረውም፡፡ አፍ አፉን እያለ አየር ያሳጣዋል። የወጣቱን አልሸነፍ ባይነትና እርጋታ ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ ሊያሳድጋቸው የሚገቡት ቀሪ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው፡፡ ይህም ሆኖ “ህዝቡ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን እንታገላለን፡፡ ከካርድም ውጭ ቢሆን፡፡” ማለቱ አወያዩን እስከ ሰማየ ሰማያት ድረስ በሚሰማ መልኩ አስጩሆታል፡፡ በተማሪ አቅሜ የገዛኋትና ሬዲዮ ለማድመጥም የምታገለግልኝ ሞባይል ስልኬ ከመፈንዳት ለጥቂት ተርፋ፣ የሁለቱን ሰዎች ትንቅንቅ ማስደመጧን ቀጠለች፡፡
እኔ የምለው አወያዩ ጋዜጠኛ ይህን ያህል ለኢህአዴግ የሚቆረቆርና የተቃዋሚዎች ሃሳብ ደሙን የሚያፈላው ከሆነ ሌሎቹ የፓርቲው ተወካዮች እዚያ መገኘታቸው ለምን አስፈለገ? ጋዜጠኛው የመጠየቅ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ እኔም እስማማለሁ፡፡ ኢህአዴግን ወክሎ የመከራከርና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሆን ብሎ ስሜት ውስጥ በመክተት (provoke በማድረግ) ክፉ ማናገር ግን አይገባውም፡፡ ይሄ ፍጹም የሆነ የአወያዩ አምባገነንነትና ማን አለብኝነት በቦታው ለነበሩት የኢህአዴግ ተወካዮችም  ንቀት ከመሆኑ በተጨማሪ ለዴሞክራሲ ስርአቱ ግንባታ ረብ የሌለው፣ የጋዜጠኝነትንም ሙያ የሚያራክስ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ እንዲህ ነው እንዴ?!
እኔ በግሌ የሰማያዊ ፓርቲን ከካርድ ውጭ አገላለፅ በአውዱ የተገነዘብኩትና ተወካዩ ያብራራውም በሌላ መልኩ ነው፡፡ ምርጫ ሲመጣ እየጠበቅን ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ሰልፎችንና ሌሎችንም መንገዶች በመጠቀም ህዝብን እናሳምናለን ነው… ያለው፡፡ ይህ ደግሞ መብትም ትክክልም በመሆኑ ከጣሪያ በላይ የሚያስጮህ አንዳችም  ነገር የለውም፡፡
ጊዜ ለኩሉ?
 አከራካሪው በጊዜ አጠቃቀም ላይ ፍጹም የሆነ አድሏዊነት ይታይበታል፡፡ የኢህአዴጉ ተወካይ አቶ መኩሪያ በአንድ ጊዜ  ከአርባ ላላነሱ ደቂቃዎች ያለማቋረጥ አውርተዋል፡፡ ተቋሚዎቹ ከአስር ደቂቃ በላይ የተናገሩበትን ጊዜ አላስታውስም። ያውም አወያዩ በረባ ባልረባው እያቋረጣቸው። አወያዩ የአየር ጊዜውንም እንደፈለገ የመጠቀም መብት እንዳለውም መታዘብ ይቻላል፡፡ “ስለሰአቱ አትጨነቁ፡፡ የቻላችሁትን ያህል እንገፋለን። እናንተን ካልሰለቻችሁ” ሲል ተደምጧል፡፡ ፅድቁ ቀርቆብኝ በቅጡ በኮነነኝ፡፡ እንኳን ሚዲያን የሚያክል ተቋም ይቅርና ዛሬ የእያንዳንዱ ግለሰብ ዘመናዊነት የሚለካው አንድም በጊዜ አጠቃቀሙ ውጤታማነት መሆኑን የዘነጋው ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዜጋው ሲያዳምጥ ውሎ ሲያዳምጥ ያለማደር መብት አለው፡፡ ሰው አዳምጦ ሊገነዘበው የሚችልበት መጠንም አለው፡፡  ሲለፈለፍ ስለተዋለ ሰው እያዳመጠ ነው ማለት እንደማይቻል መገንዘቡ የኮሙኒኬሽን ሀሁ ይመስለኛል፡፡ የማታ ማታም “የፋና ቴክኒሺያኖች ሰአት የለም አሉ” በሚል ውይይቱ ተጠናቀቀ፡፡ (እድሜ ይስጣችሁ!)
የህዝብ/ የአድማጮች ጥያቄ
ሌላው እኔን ግርም ያለኝ የህዝብ /የአድማጮች ጥያቄ እየተባሉ የሚቀርቡት ጉዳዮች ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹ በርግጥ የህዝብ ናቸው ወይ? ህዝቡስ ጥያቄ ያለው ለተቃዋሚዎች ብቻ ነው ወይ? መልስ የሚያስፈልገው የህዝብ ጥያቄ ይመስለኛል። መልሱን ግን ከዚያው ከሞጋቹ ሰው ማግኘት ይቻላል። ጥያቄዎቹ በስልክ የመጡ የህዝብ ጥያቄዎች መሆናቸውን እንደነገረን ረስቶት ራሱ ሲያብራራቸው ይቆይና ትዝ ሲለው ደግሞ ወዲያው መለስ ብሎ “ጠያቂው እንዲህ ለማለት ፈልገው አይመስሎትም ወይ?” ሲል ልባችንን ያደርቀዋል፡፡ በርግጥ ሰውዬው ጥሩ ፖለቲከኛ አይደለም፡፡ ጥሩ ፖለቲከኛ የዋሸውን አይረሳማ፡፡ ህዝቡ እንዲጠይቅ ከተፈለገ ለምን በቀጥታ በስልክ ገብቶ እንዲጠይቅ አይደረግም? ወይም ከኢህአዴግ አንጻር ችግር ይፈጥራል ብሎ ካሰበ /ማሰቡም አይቀር/ ሌሎች የውጭ ሚዲያዎች እንደሚያደርጉት ቀርጾና የማይፈልገውን አስቀርቶ አያቀርበውም? ህዝቡ ድምጹ ሳይሰማ /መናገር እየቻለ/ ጠየቀ ሲባል ትንሽ አይከብድም? ንቀትስ አይሆንም? ቆይ በዚህ በኛ ሀገር፣ ህዝብ የሚባለው የማይናገር፣  ሃሳብ የሌለው፣  ግኡዝ ነገር ሆኖ አረፈው ማለት ነው? ኧረ በህግ! የሌሎችን አተያዮችን እጠብቃለሁ፡፡ እንወያይበት!!

“ዕጣው ያልደረሰኝ… ለበጐ ነው”

    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው መጋቢት አጋማሽ ላይ 30ሺ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለከተማዋ ነዋሪዎች በዕጣ ማስረከቡን አብስሮናል፡፡ እውነትም የአፍሪካ መዲና የሆነችውና ከ4 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ይኖርባታል ተብሎ የሚገመትባት አዲስ አበባ፤ ፈርጀ ብዙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተካሄደባት የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ የከተማው አስተዳደር ከአስር ዓመት በፊት የጀመረው የኮንዶሚኒየም የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ አሁን 10ኛ ዙር ላይ ሲሆን 136ሺ ቤቶችም ለነዋሪዎች ተላልፈዋል ተብሏል፡፡
የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በመሰረቱ የድሃውን ህብረተሰብ የመኖሪያ ቤት ችግር ይቀርፋል በሚል ዓላማ የተወጠነ ፕሮጀክት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተጨባጭ ግን በሀገሪቱ በፈጣን ሁኔታ እየገሰገሰ ባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያት ፍላጎትና አቅርቦቱን ማጣጣም ባለመቻሉ፣ የመኖሪያ ቤቶቹን እየተጠቀመ ያለው ድሃው የህብረተሰብ ክፍል ሳይሆን መካከለኛ ገቢና ከዚያ በላይ የተሻለ ገቢ የሚያገኘው የህብረተሰብ ክፍል ነው። ለዚህ መቼም ሳይንሳዊ ትንተና የሚያስፈልገው አይመስለኝም። በየኮንዶሚኒየሙ የተሰቀሉ የቴሌቪዥን ሳህኖች፤ በየፎቁ ስር ተጨናንቀው የቆሙ መኪናዎችና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ከፍተኛ የኪራይ ዋጋ በቂ ምስክሮች ናቸው፡፡
ቤቶቹን ድሆች እጣው ደርሷቸው ያከራዩት… ወይም ባለእድሉ ነዋሪ ራሱ ይኑርበት ዜጎች ወጥተው የሚገቡበት ታዛ መገኘቱ በራሱ እሰየው ያስብላል፡፡
ነገር ግን ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እጣ ወጥቶላቸው መኖሪያ ቤታቸውን በአቅም ማነስ ምክንያት መረከብ ያልቻሉ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣትና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቁጠባ ባህልን ማዳበር እንዲችል ለማበረታታት የከተማ ቤቶች ልማት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደረሱት ስምምነት መሰረት፣ ባንኩ ለኮንዶሚኒየም ቤቶች መገንቢያ የሚሆን 1ቢሊዮን ብር ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት በብድር መልክ እንዲሰጥ መወሰናቸው ይታወሳል፡፡
መንግስት በጥናት ደረስኩበት ባለው መሰረት፤ በተጨባጭ የመኖሪያ ቤት ችግር ያለበት ድሃው የህብረተሰብ ክፍል እጣው በወጣለት ወቅት የሚጠየቀውን ቅድሚያ ክፍያ ማሟላት አለመቻሉን ታሳቢ በማድረግ፣ የ1997 ዓ.ም ተመዝጋቢዎችን ዳግም በመጥራት እንዲሁም አዲስ ተመዝጋቢዎችን አካቶ በሰኔ ወር 2005 ዓ.ም ላይ ባካሄደው ምዝገባ፣ ከ900ሺ በላይ ቤት ፈላጊ የከተማዋ ነዋሪዎችን እንደ አቅማቸው በ10/90፤ በ20/80 እና በ40/60 መርሀ ግብር ከፋፍሎ ወደ ቁጠባ ማስገባቱ ይታወቃል፡፡
ይሄን ተከትሎም 135 ሺህ የሚደርሱ የ1997 ዓ.ም ተመዝጋቢዎች፣ የእድሉ ቅድሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ከ21 ወራት ቁጠባና ቆይታ በኋላም ባለፈው መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓ.ም ቢያንስ ለ16 ወራት የቆጠቡ ነዋሪዎች በእጣው ተካትተው፣ 35ሺ የሚደርሱ የከተማዋ ነዋሪዎችን የቤት ባለ እድል ማድረጉን አስታውቋል፡፡ መቼም እጣው ደርሶት ያልተደሰተ፤ ያልፈነደቀ ያለመኖሩን ያህል፣ 16 ወራት መቆጠብ ባለመቻሉ ከእጣው የተገለለና ቆጥቦ እንኳን ቢሆን እጣው ያልወጣለትና ያላዘነ ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ሆኖም ግን ይህ ደስታና ሁካታ በብርሃን ፍጥነት ወደ ሀዘንና ተስፋ ማጣት ሲቀየር፣ በአንጻሩ እጣው ያልወጣለት ደግሞ “እሰየው ለበጎ ነው… እጣው የዘለለኝ” ሲል ከሳምንት ያልበለጠ ጊዜ ብቻ ነው የወሰደበት፡፡
ለምን ይሆን አትሉም?
ምክንያቱማ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ስለቤቶቹ ማስተላለፍ በበተነው ብሮሸር ላይ የተቀመጠው የቤቶቹ ሂሳብ አከፋፈል መመሪያ፣ የከተማ ልማት ሚኒስቴር በወቅቱ ተፈፃሚ ይሆናል ብሎ ቃል ከገባበት መመሪያ ጋር ተጻራሪ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ የከተማ ልማት ሚኒስትሩ በወቅቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ መንግስት ዜጎችን የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ለማድረግ በ1997 ዓ.ም የጀመረው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በሚፈለገው ፍጥነት እየተጓዘ አለመሆኑ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ እጣው የወጣላቸው ባለእድለኞች ግን ቤቱን እንዲረከቡ ጥሪ በሚደረግበት ሰዓት አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በይበልጥም ድሃው ለቅድምያ ክፍያ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ከባድ ፈተና እንደሆነበት መንግስት መረዳቱን ጠቁመው አዲስ የተዘረጋው በየወሩ የመቆጠብ አሰራር ወርሃዊ ቁጠባውን እንዲያከናውንና እጣው በወጣለት ጊዜም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መኖሪያ ቤቱን እንዲረከብ በማድረግ የአስተማማኝ ኑሮ ዋስትና እንዲያገኝ ያግዛል በማለት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ቃል ሲናገሩ፤ እያንዳንዱ ቤት ፈላጊ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ቢያንስ በየወሩ እንዲቆጥብ የተተመነበትን ሂሳብ በአግባቡ ከቆጠበ፣ እጣው በደረሰው ወቅት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ቤቱን ተረክቦ ኑሮውን ይጀምራል ማለታቸው እንደሆነ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ይገነዘባል፡፡ ነገር ግን ለ10ኛ ዙር ባለ እድለኞች የቀረበላቸው መመሪያ ግን ዱብ እዳ ነገር ነው፡፡ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት በቅርቡ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አሁን የተገነቡት ቤቶች ዋጋ የልደታ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ግንባታ ሲካሄድ የተፈጠረውን የዋጋ ልዩነት ታሳቢ በማድረግ፣ ከዚህ ቀደም ቤቶቹን ለመገንባት ይፈጃል የተባለው ተመን የ20 በመቶ የጭማሪ ማሻሻያ እንደተደረገበት አስታውቋል፡፡ ልብ በሉ! እንግዲህ ቤቶቹን የሚገነባው አካል በተፈጠረበት የዋጋ ንረት መሰረት የ20 በመቶ ጭማሪ ሲያደርግ የከተማው ነዋሪውም ከሚያገኘው ገቢ ላይ በንጽጽር የዚያኑ ያህል የዋጋ ንረት ይገጥመዋል ማለት ነው፡፡
ሆኖም የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ከሁለት ዓመት በፊት ሚኒስትሩ የተናገሩትንና ተግባራዊ ይሆናል ብለው ቃል የገቡትን ውሳኔ ወደ ጐን በመተው፣ ስለ እድለኞች የመኖሪያ ቤት ርክክብ በሚያስረዳው መመሪያ ላይ በቀረበው የዋጋ ትመና መሰረት፤ ለ10/90 ቤቶች በካሬ ሜትር 1ሺ 910 ብር፤ ለ20/80 ስቱዲዮ 2ሺ 483 ብር፤ ለ20/80 ባለ አንድ መኝታ ቤት 3ሺ 438 ብር፤ ለ20/80 ባለ ሁለት መኝታ ቤት 4ሺ 394 ብር እና ለ20/80 ባለ ሶስት መኝታ ቤት 4ሺ 776 ብር መጨመሩ ታውቋል፡፡ ከዚህ ሌላ የ10/90 ባለዕድለኞች 10 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ መክፈል ሲጠበቅባቸው፤ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ባለእድለኞች ደግሞ የ20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ መክፈል ይኖርባቸዋል ይላል፡፡ እንደ ቤቶቹ አይነትና ስፋት እያንዳንዱ ባለ እድለኛ ቅድሚያ ክፍያ እንዲከፍል የቀረበለት ተመንና ከሁለት ወር የእፎይታ ጊዜያት በኋላ በ15 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የወርሃዊ ክፍያ ተመን ጭንቅላት አስይዞ የሚያስጮህ፤ የሚያስበረግግ ምናልባትም እንደ እብድ በየጎዳናው ላይ ለብቻ እያወሩ እንዲጓዙ የሚያደርግ ነው፡፡ ለዚህ ነው አንዳንዱ ነዋሪ እጣው “እንኳንም አልደረሰኝ!!” ያለው፡፡
እንደ ማሳያ ለማቅረብ ያህል፣ ባለ ሁለት መኝታ ቤት የደረሰው ባለ እድለኛ አለ እንበል፡፡ አፍ ሞልቶ በእርግጠኝነት ይኖራል ማለት አስቸጋሪ ስለሚሆን ብቻ ዝም ብለን አለ እንበል፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ለባለሁለት መኝታ ቤት የሚከፍለው ጠቅላላ ክፍያ ብር 317068 ይሆናል፡፡ በመመሪያው መሰረት፣ 20 ከመቶ ቅድሚያ ክፍያ መክፈል ስላለበት 21 ወራት እንኳን ቆጥቧል ቢባል (560 ብር x 21 ወራት = 11,760 ብር) ይመጣል ማለት ነው፡፡ ይህ ባለ እድለኛ 51,653 ብር ገደማ ለቅድሚያ ክፍያ አቅርቦ ከንግድ ባንክ ጋር መዋዋል ይጠበቅበታል፡፡ አሁን ይሄ ብር ከየት ይመጣል? ኧረ በምን ስሌት ይሆን ከሁለት ወር የእፎይታ ጊዜ በኋላ በየወሩ 2,700 ብር ከፍሎ በ15 ዓመት ውስጥ እዳውን የሚያጠናቅቀው? ምግብ አይበላም? የትራንስፖርት ወጪ የለበትም? ለልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ አይከፍልም? እንደው በደፈናው ቤቱ ይድረሰው እንጂ ከባሌም ከቦሌም ብሎ ይክፈል በሚል የኢኮኖሚክስ መርህን በሚጥስ ስሌት ተዘጋጅቶ የቀረበ መመሪያ ነው የሚመስለው፡፡ ይሄ በእውነቱ “መንግስት አበደ እንዴ?” ያሰኛል፡፡ ግን መንግስት ቢያብድ ምን ይሆን የሚደረገው? መንግስት የኑሮውን ሁኔታና ክብደት መረዳት ይከብደው ይሆን እንዴ? የተማረ ኢኮኖሚስት ጠፍቶ ነው ወይስ የፖለቲካ ደባና ሴራ እየተካሄደ ነው? ለነገሩ ይህቺ ከተማ ለድሆች ፊቷን ካዞረች ሰነባብታለች፡፡
አንዳንዱ ሰው እኮ በአምላክ ተዓምር ካልሆነ በቀር፣ ልጆቹን እንዴት እያሳደገ እንደሆነ ማሰብ ሁሉ ይከብዳል፡፡ በዘመናዊ የሽፍን መኪና የምትመላለሱ የፖለቲካ አመራሮቻችን፤ መንግስት በአነስተኛ ክፍያ ቤት እየሰጣችሁ የምትኖሩ ባለስልጣኖቻችን፤ ልጆቻችሁን የተሻለ ት/ቤት የምታስተምሩ አለቆቻችን… እስኪ ለአንድ ወር እንኳን የእኛን የድሃዎቹን የአኗኗር ዘይቤ ኑና ተቋደሱ!!
መንግስትና አገሪቷን እየመራ ያለው ኢህአዴግ፣ በምርጫ ዋዜማ በእርግጥም ይህን አይነት የፖለቲካ ኪሳራ የሚያከናንብ ድርጊት አምኖበት ይሆን የፈጸመውን? እስኪ እውነት እንነጋገር ከተባለ መንግስት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቤቶች መስሪያ የተበደረውን 1 ቢሊዮን ብር ለማስመለስ ዋስትና ማቅረብ ይሳነዋል? የትኛውስ ኢትዮጵያዊ ነው የባንክ እዳውን መከፈል ሳይችል ቤቱ ውስጥ መኖር የሚችለው? እውነት ንግድ ባንክ እዳቸውን ያልከፈሉ ዜጎችን መኖሪያ ቤት በሃራጅ ሸጦ ብሩን ማስመለስ ያቅተዋል?
ኢህአዴግ ትላልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን እየመራ፣ እነዚህን ጥቃቅን የሆኑ፣ ነገር ግን ህዝብን የሚያማርሩ ስህተቶችን እንዴት ይፈጽማል?  በአፋጣኝ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ የሰለጠኑ አገራት አመራሮች እኮ ስህተት ተፈጽሞ ሲገኝ በይፋ ህዝባቸውን ይቅርታ ጠይቀው የእርምት እርምጃ ይወስዳሉ፡፡ እኔማ አንዳንዴ መንግስትንና ህዝብን የማቃቃር ተልእኮ ያነገቡ ጸረ ሰላም፤ ጸረ ዲሞክራሲና ፀረ ልማት ሀይሎች በመዋቅሩ ውስጥ እንዳይኖሩ እሰጋለሁ፡፡ ኢህአዴግ ሆይ፤ አሁንም የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አልረፈደም። ኧረ ጎበዝ ልብ እንበል!

በ1950ዎቹና 60ዎቹ ላይ አባ መልስ እጅጉና አባ ቼሬ አስረሴ የተባሉ የሀገር ሽማግሌዎች አራውጭኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተባለው ቦታ ይኖሩ ነበር፡፡ አራውጭኝ ጊዮርጊስ የሚገኘው በደብረ ማርቆስ አውራጃ (በቀድሞው አጠራር) በደጀን ወረዳ፣ ከደጀን ከተማ ምሥራቃዊ ክፍል ወርዶ በሚገኘው ቆላማ ቦታ ላይ ነው፡፡
አባ መልስና አባ ቼሬ በአገር የታወቁ ሽማግሌዎች ስለሆኑ አገሩ ላይ ሠርግ ሲደገስም ሆነ ተዝካር ሲወጣ አይነተኛ መራቂዎች እነርሱ ናቸው።
በአካባቢው ባህል መሠረት አንድ ሰው ተዝካር ሲጠራ፤ “በዚህን ቀን ቅጠል ይርገፍብህ” ይባላል። ለሠርግ ደግሞ “በዚህ ቀን የአዱኛዬ ተካፋይ እንድትሆን፣ የባሕር ዕቃም ይዘህ እንድትመጣ” በሚል ጥሪ ይደረጋል፡፡ የባሕር ዕቃ ማለት የጠላ መጠጫ ብርጭቆ ወይንም ብርሌ ለማለት ነው። ሽማግሌዎቹ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይም ወሳኞች ናቸው፡፡ በተለይም አባ መልስ ከልጃቸው ከቄስ አየለ መልስ የሰሙትን ይዘው እሑድ እሑድ ተዓምረ ማርያም ከተነበበ በኋላ ወንጌል ለማስተማር ይዳዳቸው ነበር፡፡ ጥቁርና ረጅም፣ ቀጭንና ሽበታም የነበሩት አባ መልስ፣ ነጭ ጭራቸውን እየነሰነሱ፤ “እናንተ ሰዎች አዋርያው ጣቢሎስ በመጀመሪያ አሂዛብ ነበር፡፡ በኋላም እዚጊሐር መረጠው ወደደው፡፡ ጦለቱም ቅድመ እዝጊሐር ደረሰለት እና እንደጣቢሎስ እንድንመረጥ ደግ ሥራ እንሥራ” ይላሉ፡፡ አዋርያ የሚሉት ሐዋርያ፣ ጣቢሎስ የሚሉት ደግሞ ጳውሎስ ለማለት ነው፡፡
አባ መልስ በጣም የዋህ ሲሆኑ አባቼሬ ደግሞ ብልጥ ናቸው፡፡ አባ መልስ በአንድ ወቅት አህያ ማነቂያ ከተባለው ቦታ በሬ ሳር ሲያበሉ፣ በሬው ወደ ገደል አፋፍ እየተጠጋ ሳር ሲነጭ በርቀት ላይ ሆነው “ወይኖ ተው ተመለስ ገደል ትገባለህ?” ይሉታል፡፡ “ወይኖ” የበሬያቸው ስም ነው፡፡ ነገር ግን ወይኖ የእርሳቸውን ምክር አልሰማ ብሎ ወደ ገደሉ እየተጠጋ ሳር ሲነጭ ዥው ብሎ ገደል ይገባና ይሞታል፡፡
በአገሬው ባህል ከብት የሞተበት፣ ሰው የሞተበትን ያህል ስለሚታይ ሰው ሊያጽናናቸው ወደቤታቸው እየሄደ “ርጥባኑን ያውርድልዎ” ሲላቸው፣
“ተውት አትዘኑ፡፡ ተው ወይኖ ገደል ትገባለህ ተመለስ ብዬ መክሬው ነበር፡፡ አልሰማኝ ብሎ ነው ገደል የገባው ተውት፣ ተውት፤ ይሉ ነበር፡፡
አባ መልስ በሕይወታቸው የዘንጋዳ እንጀራ በልተው አያውቁም፡፡ አንድ ወቅት ክፉ ቀን መጣና እህል ጠፍቶ “የዘንጋዳ እንጀራ አልበላም” ብለው ሰባት ቀን ሰነበቱ ይባላል፡፡ በሰባተኛው ቀን ሚስታቸው እማማ ሰገዱ፣ ከዘመዶቿ ጤፍ ተበድራና ተለቅታ ቀን እንዲገፋ ከዘንጋዳው ጋር ለማስፈጨት ፈልጋ፤ “አባ መልስ! ዘንጋዳውን ከጤፉ ጋር ላስፈጨው?” ትላለች፡፡
“ወዴት ወደ ህል ጠጋ ጠጋ! ነግሬሻለሁ። ጤፉን ብቻ አስፈጪው፡፡” አሉ ይባላል፡፡ አካባቢው የዝንጀሮ አገር ስለሆነ በአዝመራ ወቅት ዝንጀሮ የማይጠብቅ ገበሬ የለም፡፡ በዚያው አካባቢ ለዝንጅሮ ሁለት ስም አለው፡- አንደኛው “ሌባው”፣ ሁለኛው “ማቲው” ይባላል፡፡ ሌባው ከጓደኞቹ እየተለየ በቆሎ ዘንጋዳና ማሽላ የሚሠርቀው ሲሆን ማቲው ደግሞ በጅምላ የሚጓዘው የዝንጀሮ መንጋ ነው፡፡
ዝንጀሮ ወረራ በማድረግ ላይ መሆኑን የተረዳች አንዲት ሴት፣ አባ መልስን ከመንገድ ላይ ቆመው አገኘቻቸውና “አባ መልስ ሌባው ነው ማቲው በዚህ በኩል ያለፈው?” ትላለች፡፡
“አይ ሞኚት፤ የዝንጀሮ ሌባ እንጂ ሠራተኛ አለው እንዴ?” ብለው አሳቋት፡፡
አባ መልስ በአንድ ቅዳሜ ደጀን ገበያ ሄደው ሲመለሱ ይጉል ከተባለው ቦታ ወደሚገኘው ወደ ልጃቸው ማማው መልስ ቤት ይሄዳሉ፡፡ የልጃቸው ሚስት ደግሞ አለቅጥ ብልጥና ቅሬ ናት፡፡
“አስናቁ ተሎ በይ እህልውሃ ስጭኝ፡፡ ገበያ ውዬ ርቦኛል” ይሏታል፡፡ ሴትዮይቱ ደግሞ ሁሉም ነገር ከቤቷ እያለ የንፉግነት ባሕርይዋ አልለቃት ብሎ፤
“አይ አባቴ! እንጀራም፣ ወጥም የለም፡፡ በሞቴ እንጨት ለቃቅሜ ልምጣና እንጀራ ጋግሬ ወጥ ሠርቼ በልተው ይሄዳሉ?” ትላለች፡፡ አባ መልስም ንፉግነቷን ስለሚያውቁ፤
“በይ ተይው አስናቁ አፍሽ ቅቤ ነው፡፡ እንደበላሁ፣ እንደጠጣሁ እቆጥረዋለሁ፡፡” ብለው ወደቤታቸው ወደ አጋዥ ወረዱ ይባላል፡፡
በአገሩ ደንብ መሠረት በድግስ ወቅት ሽማግሌና ካህን የሚያበላ ሰው የተከበረና ሚስቱም ባለሙያ የሆነች መሆን አለባት፡፡ ሽማግሌና ካህን ፊት የተመረጠ ጠላና እንጀራ፣ ወጥ ነው፡፡ የሚቀርበው። እናም በአንድ ወቅት በአካባቢው ሠርግ፣ ተደገሰና አንድ ባለአፍላ (ባለጊዜ፣ ሀብታም) ሽማግሌውን አቆልቋይ ይዞ እንዲያበላ ይደረጋል፡፡ (አቆልቋይ 30 ሰው ያህል የሚይዝ አንድ የዳስ ረድፍ ነው።)  በአጋጣሚ ግን ጠላው ቅራሪ፣ እንጀራና ወጡም የማይጥም ይሆንባቸዋል ለአባ ቼሬ፡፡
በመጨረሻ ምንም ሳይመርቁ ተነሥተው ወደቤታቸው ሊሄዱ ሲል የሰውየው ሚስት (ደጋሿ)፤
“አባቴ ይመርቁኝ እንጂ?” ትላለች፡፡
“አይ አንቺ ምንሽ ይመረቃል” ብለው ጋቢያቸውን እየጐተቱ ወደቤታቸው ይሄዳሉ። በነጋታው ደግሞ እዚያው አካባቢ የተዝካር ድግስ ኖሮ ተጠርተው ወደ ዳስ ሲገቡ፣ ያ ትላንትና የማይረባ ድግስ ያቀረበው እዚያም እተዝካሩ ላይ ሌማት (አቆልቆይ) ይዞ/ኖሮ የዳስ ባላ ተደግፎ ያገኙታል፡፡ አባቼሬም፤ “አንተዬ ትላንትና እኛን ገደልክ፤ ዛሬ ደግሞ ማንን ለመግደል ነው እዚህ ቆመህ የምታደባ” አሉት፡፡
እነዚህ ሁለት ሽማግሌዎች በ1958 የጥቅምት ወር ላይ አራውጭው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ደጀሰላም ፊት ለፊት ከቅጽረ ግቢው ውጭ በሚገኝና ረጅም እድሜ በአስቆጠረ የወርካ ዛፍ ሥር የጽጌ ድግስ ሲበሉ፣ ጫኔ የተባለ ዲያቆን ልብሱን ግራና ቀኝ በመስቀለኛ መልክ አጣፍቶ አጨበጨበና፤ የሕዝቡን ሁካታና ጨዋታ ፀጥ አሰኘው፡፡ ከዚያም፣ “ስማኝ አገሬ ከ30 ዓመት በላይ በዲቁና ሳገለግልህ ኖሬያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ቅስና ተቀብለህ በቅስና አገልግለን፤ እነ ቄስ ከበደና እነ ቄስ አዳነ እያረጁ ናቸውና ቅስና ተቀብለህ እነርሱን ተክተህ አገልግለን ብትለኝ ከቄሰ ገበዙ ከአደራው አረጌ 3 ነጭ ሽልንግ እየተቀበልኩ ደ/ማርቆስ ሦስት ጊዜ ሙሉ ብመላለስም በፈተና ዜሮ በልተሃል እያሉ አባ ማርቆስ የቅስና ማዕረግ ሊሰጡኝ አልቻሉምና አገሬ ምን አርግ ትለኛለህ” አለ፡፡
ከመኻል አባ መልስ ብድግ አሉ፤ “አሄሄ እኒህ አባ ማርቆስ ምን ይከፉ ሰው ናቸው አያ? ማ ይሙት ጫኔን ጨስ ብለው ቢልኩልን ምን ነበረበት? ስማ ጫኔ አባ ማርቆስ ቢከለክሉህም እኛ ከዛሬ ጀምሮ ጨስ ጫኔ ብለንሃል፡፡ ይቀበለው እግዚሐር፤ አቡነ በሰማያት እያልክ ማሳረግ ትችላለህ፡፡” ብለው የቅስና ማዕረግ ሰጡት፡፡ በአካባቢው ያልተማረውና ፊደል ያልቆጠረው ሕዝብ፤ ቄስ ለማለት ጨስ፣ ባቄላ ለማለት በጨላ ይላል፡፡ እናም ጨስ ጫኔ የተባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
አባ ቼሬም ብድግ አሉና፤ “መልስ! ልክ ነህ፤ አሁኑኑ በእኔ ይጀመር ይፍቱኝ አባቴ” ብለው የጫኔን እጅ ሳሙት፡፡ ጨስ ጫኔም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ፈራ ተባ እያለ፣ አቡነ ዘበሰማያት እየሰጠ  ያሳርግ ጀመር። ይሁን እንጂ የጨስ ጫኔ ትምህርት እንኳን ለቅስና ማዕረግ ይቅርና ለዲቁናም በቂ ስለአልነበረ፣ ፈታኙ አሳልፎ የጐጃም ሊቀ ጳጳስ ወደነበሩት ወደ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዘንድ ሊያቀርበውና የቅስና ማዕረግ ሊያሰጠው አልቻለም፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ወርካ ኪዳነምሕረት በተባለች ቤተክርስቲያን ቄስ ታረቀኝ እና አባ ኃይሌ አወቀ የተባሉ ሰዎች ይኖሩ ነበር፡፡ ቄስ ታረቀኝ ቅዳሴ ሲቀድሱ አዘውትረው የሚመርጧት የቅዳሴ ዓይነት “ናኩተከ” የተባለችውን ኖሯል። “ናኩተከ” በጣም አጭርና ብዙ የማታስቸግር የቅዳሴ ዓይነት ናት፡፡ ኃይሌ ዐወቀ ደግሞ ሁልጊዜ ቆሞ ስለሚያስቀድስ “ነአኩተከ”ን በጨዋ አንደበቱ በቃሉ ሳይቀር ይዟታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ኃይሌ አወቀና ቄስ ታረቀኝ ይጣላሉ፡፡ አባ ኃይሌ በኃይል ሲመጡበት ኃይለኛ ነውና “አንት የናኩተክ ቄስ፣ ሰባኪ” ብሎ ይሳደባል ቄስ ታረቀኝን፡፡ ቄስ ታረቀኝ”፤ “ልባርጉልኝ ሰደበኝ” ብሎ ወደ ወረዳው ሊቀካህናት ጽ/ቤት በመሄድ ከሰሰና መጥሪያ ያመጣበታል፡፡
አባ ኃይሌም ወደ ሊቀ ካህናቱ ዘንድ በቀጠሮ ይሄዳል፡፡ ሊቀ ካህናቱም፤ “አባ ኃይሌ ቄስ ታረቀኝን የናኩተከ ቄስ፣ ሰባኪ ብለው ሰድበውታል?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ እርሱም፤
“ስድብ ውሸት፣ መናገሬ ግን እውነት ነው። አሁንስ ቢሆን የናኩተከ ቄስ ማለት ናኩተከን የሚቀድስ ማለት አይደለም ወይ? ሰባኪስ ማለት የሚያስተምር ለሕዝቡ ትምህርት የሚያስተላልፍ አይደለም ወይ?” ብሎ አባ ኃይሌ ይጠይቃል፡፡
ቄስ ታረቀኝ ደግሞ፤
“የለም የለም የናኩተከ ቄስ ያለኝ ዘልቀህ ያልተማርክ ነህ ሲለኝ ነው፡፡ ሰባኪም ያለኝ አጭበርባሪ አታላይ ማለቱ ነው፡፡ ሲል
“ውሸት፤ ናኩተከም፤ ቅዳሴ ነው፤ ሰባኪም አስተማሪ ነው” ይላል ጨዋው አባ ኃይሌ፡፡
ሊቀ ካህናቱም “አባ ኃይሌ ትክክል ናቸው፡፡ ምንም አልተሳሳቱ” ብሎ፣ ክሱን ሠርዞ፣
አባ ኃይሌን አስክሶና ሁለቱንም አስታርቆ ወደ ሀገራቸው ወርካ ኪዳነምሕረት መለሳቸው ይባላል።              

Published in ህብረተሰብ

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ኢጣሊያዊ የማፊያ መሪ (የዘራፊ፣ የመንታፊና ገዳይ ቡድን መሪ) መሞቻው ጊዜ ደርሶ ኖሮ የልጅ ልጁን ጠራው፡፡ ከዚያም፤
“የልጅ ልጄ ያስጠራሁህ ለዋዛ አይደለም፡፡ በደንብ አዳምጠኝ”
“እሺ አያቴ፡፡ ምን ልትለኝ ፈልገሃል?”
“እንግዲህ መሞቻዬ ተቃርቧል”
“አያቴ፣ ለምን እንዲህ ትላለህ?”
 “በጣም ደህና እኮ ነህ?” ምንም የህመም ምልክት እንኳ አይታይብህም
“አይመስለኝም፡፡ ድምፄ ከመክሰሙ በፊት ብታዳምጠኝ መልካም ነው፡፡”
“እሺ አያቴ አዳምጥሃለሁ”
“አየህ እኔ ምን ጊዜም እንድታስታውሰኝ ስለምፈልግ አንድ ስጦታ ልሰጥህ እፈልጋለሁ”
“አያቴ ምንም ስጦታ ባትሰጠኝም አልረሳህም”
“በጭራሽ፡፡ የሰንሰል ቅጠልም ቢሆን ሰው ለሰው ስጦታ የሚሰጠው እንዲያስታውሰው ይጠቅመዋል፡፡ ስለዚህ ኮልት 45 ሽጉጤን እሰጥሃለሁ፡፡ ዘራፊ፣ መንታፊና የገዳይ ቡድን አባል የሆንኩትን አያትህን ምን ጊዜም የምታስታውሰኝ በዚህ ሽጉጥ ይሆናል” አለ፡፡
ይሄኔ የልጅ ልጁ፤
“ግን አያቴ፣ እኔ ሽጉጥ፣ ጠመንጃ፣ ጦር ጋሻ አልወድም፡፡ ምን ያደርግልኛል? እኔ የማፊያ ቡድን አባል አልሆንም፡፡  ይልቅስ ዕውነት የምትወደኝ ከሆን ሮሌክስ ሰዓትህን ትተህልኝ ሂድ፡፡ ውድ ሰዓትህ ሁልጊዜ አንተን የስታውሰኛል፡፡”
አያትዬው ድምፁ እየተንተባተበና እየተጎተተ መጣ፣
“የልጅ .. ል…ጄ…. በደ…ምብ አድምጠኝ የ… ቤታ…ችንን… ን.ግ.ድ.የምትመራው አንድ…ቀን አን…ተ  ነ.ህ… ከዚያ ቆንጆ ..ሚ..ስ..ት…ታገባ…ለህ፡፡ ብዙ … ገንዘብ ..  ይኖ.. ርሃል፡፡ ትልቅ ቪላ.. ቤ..ት ይኖር…ሃል፡፡ ምናል…ባ…ት..ም.. አንድ ሁለት ባምቢኖ (ልጆች) ይኖሩሃል፡፡
… እና ከዕለ… ታት አንድ ቀን … ሥ…ራ ውለህ ወደ ቤት … ስትመጣ ሚስትህ … ከሌላ ወንድ ጋር ተኝታ ልታገኛት ትችላለህ…  ያን ጊዜ ምን ታደርጋለህ? … የእኔን ሮሌክስ ሰዓት እያሳየህ “በቃችሁ ሰዓቱ ደርሷል!” ትላቸዋለህ?
ይልቅ መሳሪያዬን ተረከብ!” አለውና ድምፁ መሰማት አቆመ፡፡
*            *           *
ሁሉም ጉዳይ የየራሱ ማስፈፀሚያ አለው፡፡ የሀገራችን አንዳች የሚያህል ችግር አባትና ልጅ፣ ትውልድና ትውልዱ አለመጣጣሙ ነው፡፡ የአንዱ ፍላጎት ከሌላው ፍላጎት ጋር አለመመጋገቡ ነው፡፡ ለማንኛውም እያንዳንዱ ትውልድ የየራሱን ጣዕም ማበጀቱ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የየራሱ ጣዕም የሌለው ትውልድ ለአገር አይበጅም፡፡ ስፖርት የሚያዘወትር፤ ትግል የሚወድ፣ አለ፡፡ ባንፃሩ ማጭበርበርን እንደኑሮ ዘዴ የለመደ፣ በመፈክር አገር እገዛለሁ ብሎ የሚያስብ፤ እርስ በርስ መጠላለፍን እንደፖለቲካ ካባ የደረበ ወዘተ ብዙ ዓይነት ትውልድ አይተናል፡፡
ሁሉም እኔ ልክ ነኝ ስለሚል ተው አይሆንም ማለት አዳጋች ነው፡፡ አቋሙ ታሪክ እስኪሆን በትዕግስት እንድንጠብቅ እንገደዳለን፡፡
ሌላው ችግራችን ስም-ልጠፋ ነው - በክፋት፡፡ (Branding) በዚህ ጉዳይ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ያለንን መስማት ጥሩ ነው፡-
“አንድ ተረት ልንገርህ፡፡ አንዲት እናት ልጇ አይናፋር ኖሮባት ከጓዳ አልወጣ አለ፡፡ “ወጣ በል!”  ተብሎ ከጓደኞቹ ጋር መቀላቀል ቢፈልግም አልቻለም፡፡ ግን የልጆቹን ሁሉ ስም አጥንቷል፡፡ እዚያ አካባቢ የሚነገረውን ስለሚሰማ ሁሉን ያውቃል፡፡ እቤት ይገባና ለእናቱ “በደሻ እንዲህ ሲል አፍንጮ እንዲህ ብሎ መለሰለት … ቀዮ ግን …” እያለ ይነግራታል፡፡ እናቱ ስትመልስለት “ያንተስ ስም ማነው?” ስትለው “እኔማ … እኔማ ስም የለኝም” አላት፡፡ “እንግዲያው ሂድ… ሂድ መንገዱን አቋርጥ፡፡ ልክ ስታቋርጥ ስም ያወጡልሃል፡፡ ያኔ ትነግረኛለህ፡፡” አለችው፤ ይባላል፡፡
መንገዱን ማቋረጥ የሀሳብ ትግል ይሆናል፡፡ የአቋም መለወጥ ሊሆን ይችላል። የሀሳብ ልዩነትን ግልፅ ሆኖ ማሳየት ሊሆን ይችላል፡፡ በማንኛውም የትኛውንም አዲስ መንገድ አቋርጠን እንሂድ ብንል አዲስ ስም እንደሚወጣልን ጥርጥር የለውም፡፡ ያየናቸው መንግስታት ሁሉ ለጠላቶቻቸው ስም ሳያወጡ አልኖሩም፡፡ ንፁሃን ዜጎችን ጭምር ስም ያወጡላቸዋል፡፡ ይሄ ደግ ዜጋ መንግስትን እንዳያምንና እንዲጠራጠር ያደርገዋል፡፡ ጥርጣሬ ካለ ዕድገት የለም፡፡ ልማት የለም፡፡ ወደፊት መራመድ የለም! ስለዚህ ለትንሽ ለትልቁ መንገድ አቋራጭ፤ ስም ማውጣቱን ትተን ለምን ከቤቱ ወጥቶ መንገድ አቋረጠ? ብለን መጠየቅ ያባት ነው!
ለውጥ ባየን ቁጥር ግትር ብለን አልቀበልም ማለት ጅልነት ነው፡፡ ለውጥ ባየን ቁጥር አብረን ዘራፍ ማለትም ጅልነት ነው፡፡ እኔ ምን አገባኝ ብሎ በምንግዴ መጓዝና መንግሥት ተለወጠ  አልተለወጠ፣ አይሞቀኝ አይበርደኝ ማለት የባሰ ጅልነት ነው! እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው ማለት እንደማያዋጣን ከልብ አውቀን ከተጓዝን አያሌ ነገሮችን ወደቀናው ነገ እንዲያመሩ ለማድረግ እንችላለን፡፡ ለዳግማይ ትንሣዔም እንበቃለን! መልካም በዓል!




Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 7 of 17