(የአሜሪካውያን ነገር! መፍትሄ ይዞ ብቅ የሚል አይጠፋም። ሚቸል ክሮዝቢ፣ የፍቺ ወጪዎችን በሶስት እጅ የሚቀንስ ዘዴ በመፍጠር ቢዝነስ ጀምራለች።) አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት መኖሪያ ቤት የነበራቸው ባልና ሚስት፣ በፍቺ ሲለያዩ የፈጠሩትን ፀብ ልንገራችሁ። እንደ ምርጫቸው አንድ አንድ መከፋፈል ይችሉ ነበር። ባል አንደኛውን ቤት መረጠ። ሚስት ምንም አልከፋትም። የመኖሪያ ቤቶቹ ዋጋ ተቀራራቢ ስለሆነ፣ ሌላኛውን ቤት መረጠች። በቃ? በጭራሽ! ሚስትዬው ያለምንም ጣጣ ስለተስማማች፣ ባልዬው በቁጭትና በእልህ ተነሳስቶ ሃሳቡን ቀየረ። እንለዋወጥ አለ - ሚስትን ለማሳረር በመመኘት።

የራሱን ጥቅም ሳይሆን፣ የሚስቱን ጉዳት ለማየት ነው የናፈቀው። በእርግጥ ሚስትዬው፣ አንደኛውን ቤት እስካገኘች ድረስ ግድ አልነበራትም። ግን እልህ ውስጥ ገባች፤ “አይሆንም!” አለች። ሁለቱን ለማስታረቅ ያልተደረገ ሙከራ ባይኖርም አልተሳካም። ስለዚህ መኖሪያ ቤቶቹ ተሸጠው በገንዘብ እንዲከፋፈሉ ተወሰነ። አቶ ባል፣ ነገርዬው እንዲህ እየከረረ እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርስ አልመሰለውም ነበር። ግን፣ የተበላሸውን ነገር መልሶ ማስተካከል አይችልም። ቤት የሚገዛ ሰው ፈልገው ማምጣት አለባቸው፤ ወይም ደግሞ በፍርድ አፈፃፀም መስሪያ ቤት በኩል፣ በሃራጅ ቤቶቹ ይሸጣሉ። ያው፤ ለሃራጅ የቀረበ ንብረት ብዙም ዋጋ አያወጣም። ለዚህም ነው፤ ባልዬው ቤት የሚገዙ ሰዎችን አፈላልጎ ያመጣው። ይህን ሁሉ ጣጣ በመፍጠሩ የተበሳጨችው ሚስትዬው ግን ፈቃደኛ አልሆነችም። በሃራጅ ካልተሸጠ ሞቼ እገኛለሁ አለች። የራሷን ጥቅም ከማስላት ይልቅ፣ የባልዬውን መክሰር ለማየት ጓጉታለች።

ከፍርድ አፈፃፀም ሰራተኞች እንደሰማሁት፣ ቤቶቹ በሃራጅ ስለተሸጡ ሁለቱ ሰዎች ወደ 300 ሺ ብር ገደማ ከስረዋል። ከፍቺ ጋር አላስፈላጊ እልህ የሚፈጠረው በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። የትም አገር ቢሆን፣ ትዳር በፍቺ ሲፈርስ፣ ብዙውን ጊዜ አዲስ ጥላቻና ቂም ያበቅላል። ባለትዳሮቹን ለፍቺ ከገፋፋቸው ጥላቻ ይልቅ፣ ለመፋታት ከወሰኑ በኋላ በንብረት ክፍፍልና በልጅ አስተዳደግ ጉዳዮች ላይ ሲከራከሩ የሚፈጠረው ጥላቻ የባሰ ነው። በእርግጥ በሰለጠኑት አገራት፣ የፍቺ ጣጣዎችን በስርዓት ለማስኬድና የመናቆር ስሜቶችን ለማብረድ፣ ባልና ሚስት የህግ ባለሙያዎችን (ጠበቆችን) ይዘው ነው የሚከራከሩት ወይም የሚደራደሩት። ግን፣ ይሄም ቢሆን ወጪው ቀላል አይደለም። አሜሪካ ውስጥ፣ በፍቺ የሚለያዩ ጥንዶች፣ እያንዳንዳቸው በአማካይ 10 ሺ ዶላር ለህግ አማካሪ ይከፍላሉ። አንድ ትዳር ሲፈርስ 20 ሺ ዶላር ለጠበቆች ክፍያ ይውላል ማለት ነው። ሌሎች ወጪዎች ተጨምረውበት፣ በአሜሪካ የፍቺ ነገር በአመት 30 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚፈጅ፣ ሰሞኑን የወጣው የፎርብስ መፅሄት ገልጿል።

ምን ያህል ሰው በዚህ ወጪ እንደሚቸገር አስቡት። የቢዝነስ ስራ ዋነኛ ባህርይ፣ “ችግሮችን የሚያቃልልና ወጪዎችን የሚቀንስ መፍትሄ” ማቅረብ አይደል? ይሄውና፣ የ37 አመቷ ሚቸል ክሮዝቢ፣ የፍቺ ወጪዎችን በሶስት እጅ የሚቀንስ ዘዴ በመፍጠር የቢዝነስ ስራ ጀምራለች። ጥንዶች ለፍቺ ከሃያ ሺ ዶላር በላይ ማውጣት አይኖርባቸውም። ከ7ሺ ዶላር ባነሰ ወጪ ጉዳያቸውን በድርድር ይጨርሳሉ። በዚያ ላይ ደግሞ፣ ከተጨማሪ ቂምና ጥላቻ ይድናሉ የምትለው ክሮዝቢ፣ በቢዝነሷ ስኬታማ በመሆኗ ባለፉት ጥቂት ወራት ድርጅቷ አንድ ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል - ፎርብስ እንደዘገበው።

መቼስ፣ ፍቺ ከተፈፀመ አይቀር፣ ወጪንና ጥላቻን የማያባብስ ዘዴ ሲገኝለት መልካም ነው። በአሜሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጋብቻና ፍቺ የሚፈፅሙ ሰዎች ከጠቅላላ የህዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀሩ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መጥተዋል። ከሃያ አመት በፊት፣ ከአስር ሺ ሰዎች መካከል በአመት 98 ጋብቻዎች እና 47 ፍቺዎች ይፈፀሙ ነበር። ዛሬ የጋብቻዎቹ ቁጥር ወደ 68፣ የፍቺዎቹ ቁጥር ደግሞ ወደ 34 ቀንሷል። በአጠቃላይ ግን ባለፈው አመት በምድረ አሜሪካ ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ጋብቻዎችና ወደ ዘጠኝ መቶ ሺ ገደማ ፍቺዎች ተፈፅመዋል። የአውሮፓም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፤ በአመት 2.2 ሚሊዮን ጋብቻዎችና አንድ ሚሊዮን ገደማ ፍቺዎች ይፈፀማሉ።

Published in ዜና

በፖለቲካ ግጭትና በገንዘብ እጥረት ሳቢያ የተጓተተው የዚምባብዌ ምርጫ፣ በደቡብ አፍሪካ ሸምጋይነትና በ100 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እርዳታ ቢታገዝም፣ እንደገና ከመራዘም አለመዳኑን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል። ለሰኔ ወር ታስቦ የነበረው ምርጫ፣ ወደ ሐምሌ፣ ከዚያም ወደ መጪው ጥቅምት ወር ተሸጋግሯል። በአልማዝ ማዕድን፣ በብረት ምርት፣ በእህል ኤክስፖርትና በሌሎች ጠንካራ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ትታወቅ የነበረችው አገር፣ እንጦሮጦስ የወረደችው በጥቂት አመታት ውስጥ ነው። ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የሚመሩት መንግስት፣ የግለሰቦችን ንብረት እየወረሰና አለቅጥ ገንዘብ እያተመ፣ በ10 አመታት ውስጥ አገሪቱን የረሃብና የስራ አጥነት መናኸሪያ አድርጓቷል። የራሷ የገንዘብ ኖት የሌላትና ምርጫ ማካሄድ የማትችል የቀውስ መንደር የሆነችው ዚምባብዌ እንደአወዳደቋ በፍጥነት፣ ቶሎ ልታገግም ትችላለች ተብሎ አይታሰብም።

ዚምባብዌ፣ እንደ ሶማሊያ ወይም እንደ ኮንጎ በለየለት ጦርነት ውስጥ ሳትዘፈቅ፤ “በመንግስት ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሾቀች አገር” በመሆኗ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ለየት የምትል ትመስላለች። ለዚህም ነው፣ የአውሮፓ አገራትና አሜሪካ በሙጋቤ መንግስት ላይ፣ የተለያዩ ማዕቀቦችን የጣሉት። ነገር ግን፣ የመጠንና የደረጃ ጉዳይ ካልሆነ በቀር፣ ዚምባብዌ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ብዙም አትለይም። እጅግ ገዝፈውና ገንነው የሚታዩት የዚምባብዌ ሁለት ዋና ዋና ችግሮች…፣ ያው በሌሎች የአፍሪካ አገራትም ዘወትር የሚታዩ ችግሮች ናቸው። በአንድ በኩል፣ በፖለቲካ አፈናና ግጭት የምትናጥ አገር ነች - እንደ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት። በሌላ በኩል ደግሞ የግል ቢዝነስን እንደ ጠላት የሚፈርጅ መንግስት፣ አለቅጥ ገንዘብ ማተምንና የውጭ እርዳታን የለመደ ነው - ይሄም በበርካታ የአፍሪካ አገራት የሚታይ ችግር ነው። የኬቶ ኢንስቲቱይት ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የዚምባብዌ መንግስት በየአመቱ ብዙ የገንዘብ ኖት የማተም አባዜው እየተባባሰ የመጣው የዛሬ 15 አመት ገደማ ነው።

ከዚያም በፊት ቢሆን፣ ከልክ ባለፈ የገንዘብ ህትመት ሳቢያ “የዚምባብዌ ዶላር” ቀስ በቀስ ዋጋ እያጣ ነበር። በየአመቱ የሸቀጦች ዋጋ ከአስር እስከ ሃያ በመቶ እየናረ ቆይቷልና። በኢትዮጵያና በሌሎቹ የአፍሪካ አገራት በየጊዜው ከሚታየው የዋጋ ንረት አይለይም። እ.ኤ.አ ከ1998 በኋላ ግን፣ የገንዘብ ህትመቱ ይበልጥ እየጨመረ መጣ። እናም፣ ሃያ በመቶ የነበረው አመታዊ የዋጋ ንረት፣ ወደ 48% ዘለለ። መንግስት የገንዘብ ህትመቱን አደብ ሊያስገዛ ባለመፈለጉ፣ በቀጣዩ አመት የዋጋ ንረቱ ባሰበት - ወደ 60% ተጠጋ። እንደእብደት ሊቆጠር ይችላል። ግን፣ በአገራችንም ሚሊዬነሙ መባቻና የዛሬ ሁለት አመት የታየው የዋጋ ንረት፣ ስድሳ እና አርባ በመቶ ገደማ የደረሰ እንደነበር አስታውሱ። በእሳት መጫወት ይሉሃል ይሄ ነው! ለምን ቢባል፣ የገንዘብ ህትመት በጊዜ ካልተገታ፣ አብዛኛው ሰው በአገሬው ገንዘብ ላይ እምነት እያጣ፣ የዋጋ ንረት ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል።

በዚምባብዌ ለሶስተኛ አመት ከሃምሳ በመቶ በላይ የሆነ የዋጋ ንረት ከተመዘገበ በኋላ ነው ነገር የተበላሸው። በ2001 የዋጋ ንረት ከእጥፍ ላይ በማሻቀቡ ኢኮኖሚው ተመሳቀለ። ከዚህ በኋላ መንግስት ሊቆጣጠረው አልቻለም። አዙሪት ውስጥ እንደመግባት ነው። በገንዘብ ህትመት የተነሳ ዋጋ ይንራል። በዋጋ ንረት ሳቢያ የመንግስት ወጪ ያሻቅባል። ወጪውን ለመሸፈን ገንዘብ ስለሚያትም የዋጋ ንረቱ ይባባሳል። በዚህ አዙሪት ውስጥ የገባው መንግስት፣ በዚያው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ አምስት መቶ ኖት አሳተመ። በቀጣዩ አመት የዋጋ ንረት በእጥፍ ጨመረና 200% ደረሰ። መንግስት ባለ አንድ ሺ ኖት አሳተመ። የዋጋ ንረት ወደ 600% ተወረወረ። አንዴ ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ በኋላ፣ እንደ ገና ወደ ጤንነት ለመመለስ ዳገት ነው። ያኔ፣ መንግስት ባለ 5ሺ፣ ከዚያ ባለ10ሺ፣ ከዚያም ባለ20ሺ ኖት አሳተመ - በሶስት ወራት ልዩነት። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ባለ ሃምሳ ሺ! የመቶ ሺ ኖት በታተመበት በ2006፣ የሸቀጦች ዋጋ በአመት ውስጥ በ12 እጥፍ ጨመረ። በ1998 ከነበረው የሸቀጦች ዋጋ ጋር ከተነፃፀረማ፣ የትየለሌ ነው። አንድ የዚምባብዌ ዶላር ይሸጥ የነበረው ክብሪት፣ ዋጋው ወደ ሰላሳ ሺ አሻቅቧል። በዚህ አላቆመም።

በቀጣዩ አመት መንግስት ባለ “ሁለት መቶ ሺ ኖት” ማሳተም ጀመረ። በወር ልዩነት የሩብ ሚሊዮን እና የግማሽ ሚሊዮን ኖቶች በገፍ ታተሙ። የዋጋ ንረት በአንድ አመት ውስጥ በስድስት መቶ እጥፍ ጨመረ። የዚምባብዌ መንግስት የ2008 አዲስ አመትን የተቀበለው ባለ ሚሊዮን ኖት በማሳተም ነው። ከዚያማ ተዉት። ወር ሳይሞላው ባለ አምስትና ባለ አስር ሚሊዮን ኖቶችን አምጥቶ አገሬው ላይ አራገፈው። ሁለት ወር ቆይቶ፣ በባለ 25 እና በባለ 50 ሚሊዮን ኖቶች አገር ምድሩን አጥለቀለቀው። አመቱ ሳይጋመስ፣ የመቶ ሚሊዮንና የአምስት መቶ ሚሊዮን ኖቶች ከታተሙ በኋላ፣ ባለ ቢሊዮን ኖት መጣ። አገር ጉድ አለ። የ25 እና የ50 ቢሊዮን ኖቶች እየታተሙ መሆናቸው አልታወቀም ነበር። የመቶ ቢሊዮን ኖት ደረሰ። በዚህ ወቅት “የዋጋ ንረት የት ደረሰ?” ብሎ ለማስላት መሞከር በጣም ከባድ ሆኗል - የሸቀጦች ዋጋ በየሰዓቱ ስለሚንር። የትሪሊዮን ኖቶች የመጡት በአዲስ አመት ነው - በ2009። በአመቱ የመጀመሪያው ወር ላይ፣ ዚምባብዌ የአለም ሪከርድ ሰበረች።

እስከዚያው ድረስ በአለማችን ከተመዘገቡት የዋጋ ንረት እብደቶች ሁሉ የባሰና፣ 14 ዜሮዎች የተደረደሩበት ባለ መቶ ትሪሊዮን ኖት አሳተመች። ግን ዋጋ የለውም። አንድ ሺ ያህል ባለ መቶ ትሪሊዮን ኖቶች ይዞ፣ አንዲት ዳቦ መግዛት አይቻልም። አብዛኛው ሰው፣ የአገሬውን ገንዘብ መጠቀም አቁሟል። በውጭ ምንዛሬ መገበያየት በአዋጅ ቢከለከልም፣ ሰዉ ሁሉ በዶላርና በዩሮ ብቻ የሚጠቀም ሆኗል። ምንም ማድረግ ስላልተቻለ፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ መንግስትም በዶላርና በዩሮ መጠቀም ጀመረ።

አገሪቱ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የራሷ ገንዘብ የላትም። አዲስ አመትን በአዲስ የገንዘብ ህትመት መቀበል የለመደው የዚምባብዌ መንግስት፣ የእንጦሮጦስ ጉዞውን መቀጠል አልቻለም። እናም ዘንድሮ፣ በአዲስ አመት የመንግስት ካዝና ውስጥ የነበረው ገንዘብ 217 ዶላር ብቻ ነበር። ምርጫ ለማካሄድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ከየት ይምጣ? እርዳታ ነዋ። አገሪቷ ግን በአልማዝ ማዕድን ከበለፀጉት የአለማችን አገራት መካከል አንዷ ነች። ነገር ግን፤ ኢኮኖሚን ለማቃወስ “የሚተጋ” መንግስት ባለበት አገር፣ መስራትና ማምረት ከባድ ነው። ከተመረተም፣ የዝርፊያና የሙስና ሲሳይ ነው የሚሆነው።

Published in ዜና
Page 14 of 14