ዊኒ ባይናይማ የመጀመሪያዋ የዩጋንዳ ሴት የአውሮፕላን ኢንጂኒየር ናት፡፡ ሙሴቬኒ የሚልተን ኦቦቴን አገዛዝ ለመጣል ባደረጉት የአምስት አመታት ትግል ጫካ በመግባት ዊኒ፤ ከድል በኋላም የፓርላማ አባል ሆናለች። በአሁኑ ወቅት የኦክስፋም ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር በመሆን እየሰራች ትገኛለች። ከሙሴቬኒ ጋር በአንድ የትውልድ ቀዬ የልጅነት ጊዜዋን ያሳለፈችው ዊኒ፤ ጫካ ሳሉ የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው፡፡ መንግስት ተመስርቶ ሙሴቬኒ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ በተፈጠረ አለመግባባት ከፓርቲው ወጥታ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች መስራት ጀመረች፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የሙሴቬኒ የግል ሀኪም ከነበረውና ከትግሉ በኋላ የተቃዋሚ ፓርቲ ከመሰረተው ኪሳ ቢሲጂ ጋር ጋብቻ መስርታለች፡፡ ዊኒ ከትጥቅ ትግል በኋላ ውጤታማ ከሆኑ ጥቂት አፍሪካውያን ሴቶች አንዷ ናት። ሰሞኑን በአዲስ አበባ በነበራት ቆይታ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት ዕቁባይ ጋር ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

እስቲ ራስሽን አስተዋውቂ… ዊኒ ባይናይሚ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም በምስራቃዊ ኡጋንዳ በሚገኘው ምባራራ የተባለ ሥፍራ ነው። በኤሮኒውቲካል ኢንጂነሪንግ የመጀመርያ ዲግሪዬን አግኝቻለሁ፡፡ አሁን ከገበያ በወጣው ኤየር ዩጋንዳ በኢንጂነርነት አገልግያለሁ፡፡ የኢኒጂነርነት ስራሽን የተውሽው ያኔ በዩዌሪ ሙሴቪኒ የተጀመረውንና የሚልተን አቦቴን አገዛዝ ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል ውስጥ ለመሳተፍ ነው፡፡ ወደ ጫካ ለመግባት እንዴት ወሰንሽ? ዩጋንዳ በኤዲ አሚን እና በሚልተን አቦቴ አምባገነን አገዛዞች ብዙ ስቃይ አሳልፋለች፡፡ በወቅቱ እኔ እንግሊዝ አገር ነበርኩ፡፡ ይህን አስከፊ ስርአት ለማስወገድ ሙሴቪኒ የትጥቅ ትግል ሲጀምር እርምጃው ጥሩ ነው ብዬ ተቀብዬ ነበር። ከዛም ባለፈ የድርሻዬን ማበርከት እንዳለብኝ ስላመንኩ ትግሉን ተቀላቀልኩ፡፡ መጀመሪያ ላይ ሴቶች ጫካ ገብተን አልነበረም የምንታገለው፡፡

እኔና በለንደን ይኖሩ የነበሩ ሌሎች ሴቶች ለትግሉ የሚሆን ድጋፍ በማሳባሰብ እናግዛቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ከሩቅ ሆኖ መታገሉ ራሱ አገልግሎት ቢሆንም ጫካ መግባት እንዳለብኝ በመወሰን በ22 አመቴ ጫካ ገባሁ፡፡ ውሳኔዬን ግን ሙሴቪኒ አልተቀበለውም ነበር፡፡ ለምን ነበር ያልተቀበሉት? በጫካ ያለው ሁኔታ ለሴቶች ጥሩ አይደለም በሚል ምክንያት ነው፡፡ ጫካ ከምትገቢ ዚምባቡዌ ወይም ዩጋንዳ ውስጥ ሆነሽ ለትግሉ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሚስጥር አድርጊ ብሎ መከረኝ፡፡ እኔ ግን ፈቃደኛ አልሆንኩም፤ እዛው ጫካ ውስጥ ሆኖ መታገልን መረጥኩ፡፡ የትግል ህይወት እንዴት ነበር? እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ለሴቶች ከባድ ነበር፡፡ ግን እወጣዋለሁ ብዬ ስለገባሁ ተቋቁሜዋለሁ፡፡ የሚልተን አቦቴን አገዛዝ ለመጣል የተደረገው የትጥቅ ትግል አምስት አመት ፈጅቷል፡፡ የትጥቅ ትግሉ ካበቃ በኋላስ? እ.ኤ.አ በ1995 ዓ.ም የዩጋንዳ ህገመንግስት ሲፀድቅ የአርቃቂ ቡድኑ አባል ነበርኩ፡፡

ለሁለት ተከታታይ የስራ ዘመኖች የፓርላማ አባል በመሆን አገልግያለሁ፡፡ በፈረንሳይ የዩጋንዳ የዩኔስኮ አምባሳደርም ነበርኩ፡፡ የአፍሪካ ህብረት የስነፆታ እና የልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን በህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ሠርቻለሁ፡፡ ባለፈው ሚያዝያ ወር የኦክስፋም ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ሆኜ ከመሾሜ በፊት፣ በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የልማት ፖሊሲ ቢሮ የስነፆታ ዳይሬክተር በመሆን አገልግያለሁ፡፡ ከታገልሽበትና የትጥቅ ትግሉን ከመራው “ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት” የወጣሽው በሰላም እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ እስኪ ስለሱ አጫውቺኝ… እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም ከንቅናቄው የኢንፎርሜሽን ዳሬክተርነት እንድነሳ ተደረግሁ። ምክንያቱ ደግሞ ለፓርቲው ውሳኔ እና ፖሊሲ ታዛዥ አይደለችም የሚል ነው፡፡ በፓርላማ ቆይታዬም በተለይ ከሙስና ጋር በተያያዘ የማነሳቸው ጉዳዮች ብዙም ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ነው የወጣሁት፡፡

የታገላችሁለትን አላማ አሁን ካለው አጠቃላይ የዩጋንዳ ሁኔታ ጋር ስታይው ምን አስተያየት ትሰጫለሽ? አሁን የማወራሽ የአለምአቀፍ ድርጅት ተወካይ ሆኜ ስለሆነ ስለዩጋንዳ ፖለቲካ አላወራም፡፡ በአጠቃላይ ግን ዩጋንዳ ልክ እንደብዙዎቹ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች በብዙ ችግሮች የተተበተበች አገር ናት፡፡ ድህነት፣ ኋላቀርነት… ሁሉም መፍትሔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የማልረሳው የምትይው መጥፎ ትዝታ ምንድን ነው? ለምን መጥፎውን ትጠይቂኛለሽ፡፡ እኔ የማልረሳውን ጥሩ ትዝታዬን ነው የምነግርሽ። ከጫካ መጥተን ዋና ከተማዋን ካምፓላን እንደተቆጣጠርን አንድ ሚሽን ተሠጥቶኝ ወደ አንድ ጣቢያ ሄድኩ። እንደደረስኩ በሩ ላይ ያለው ጥበቃ አንዳንድ የሴኩሪቲ ጥያቄዎችን ጠየቀኝ፡፡ መለስኩለትና ውስጥ ልገባ ስል ቆይ ሃላፊዬን አግኚ አለኝ፡፡ ቆሜ ጠበቅሁ፡፡ አንዲት ሴት ወታደር ወደ እኔ መጥታ ሠላምታ ሰጠችኝ፡፡

ሴትየዋ ከአራተኛ ክፍል በላይ የዘለለ ትምህርት አልተማረችም፡፡ በሀላፊነት የያዛቸው ጣቢያ ግን በወቅቱ በአገሪቱ ብቸኛ የነበረውንና ብዙ ምሁራን የሚወጡበትን የማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይሄን እንቆቅልሽ ሁልጊዜ ሳስበው ይገርመኛል፡፡ ከዛ ወጣ ብዬ ሳስበው ደግሞ እነዚህ ሴቶች ያለ እንቅልፍ ያሳለፏቸው ሌሊቶች፣ መስዋዕትነቶች፣ ከማህበረሰቡ አስተሳሰብ ጋር ተያይዞ የሚደርስባቸው ችግር አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡

የኢንጂነርነት ትምህርትሽ ምን ላይ ደረሰ? የትጥቅ ትግሉ እንዳበቃ በክሬንፊልድ ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ኢንጂኒሪንግ፣ “ኢነርጂ ኮንሰርቬሽን” ላይ የማስተርስ ዲግሪዬን ሰርቻለሁ። የአፍሪካ ህብረት የ50ኛ አመቱን የወርቅ ኢዮቤልዩ እያከበረ ነው፡፡ በአሉ ሲከበር መረሳት የሌለበት የምትይው ዋነኛ ጉዳይ ምንድን ነው? የአፍሪካ ህብረት የአባል አገሮች ስብሰባ ነው፡፡ እያንዳንዱ አገር የህዝቡን ጥያቄዎች የሚመልስበት፣ የአፍሪካውያንን ሰቆቃ፣ ስደት እና ረሀብ ለማስቆም በቁርጠኝነት ቃል የሚገባበት ወቅት መሆን አለበት። አፍሪካ የሀብቷ አዛዥ መሆን መጀመር አለባት። ህዝቦቿ የማይጨበጥ ተስፋ ሊሰጣቸው ሳይሆን የሚጨበጥ ተስፋ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

የአፍሪካ አገሮች ጠበል ጠዲቅ ‘አብረው መቃመስ’ ከጀመሩ ‘ፊፍቲ’ ሞላቸው አይደል! እሰይ…ሌላ ‘ፊፍቲ’ ዓመት ያሰንብታቸው፡፡ ታዲያ ለብዙዎቹ ይቺ የሀበሻ ቅኔ ትተላለፍኝማ! መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ ሲገሠግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጂ… አዎ…ያነሳ ቀን መልሶ እንደሚያፈርጥ ማወቅ አሪፍ ነው፡፡ (የጋዳፊና የሙባረክ ችግር ይሄን ነገር ተርጉሞ የሚያቀርብላቸው ያለመኖሩ ነው፡፡ ልክ ነዋ! አይደለም ሰው…‘ጫፍ’ ላይ ያለ ድንጋይም ቀኑ ሲደርስ ተንከባሎ ለኮብልስቶን ጥሬ ዕቃ ይሆናል፡፡) እናማ…ጥያቄ አለን…‘የሚደርሰን’ ጠበል ጠዲቅ ካለ ይድረሰና! ዘላላም እኮ ‘እዛ ላይ’ አይከረምም፡፡ የእኛ ወዳጅነት የሚፈለግበት ጊዜ ይመጣላ! ሲወጡ የተጠየፉን ሲወርዱ “ማሬ…” “ወርቄ…” አይነት ነገር ጊዜው አልፎበታል፡፡

መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ ሲገሰግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጂ፣ የሚባል ነገር አለ፡፡ አዎ፣ እዚቹ ክፍለ አሀጉራችን ውስጥ በአብዛኛው የሚያነሳውም፣ የሚጥለውም ‘ቀን’ ነው፡፡ የተጠቀሱት ነገሮች እንደ ‘ጎልድን ጁብሊ’ አከባበር ግለሰባዊ አስተዋጽኦ ይታይልንማ! እኔ የምለው… ድሮ ‘ካዛብላንካ ቡድን’ ምናምን የሚባሉ ቡድኖች ነበሩ አይደል! ዘንድሮ ‘ምናምኖፎን…’ ነገር የሚባሉ “የቡድንና የቡድን አባቶች” ነገር አለ እንዴ! አሀ…ስለሚመለከተን መጠየቅ አለብና! እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ድሮ ለኳስ ቡድን ሲመሰረት አሪፍ ዘዴ ነበረው፡፡ ሁለት ልጆች ይያዛሉ፣ ስም ይከፋፈሉና የቡድን አባቶች ዘንድ ይሄዳሉ፡ “የቡድንና የቡድን አባቶች…” “ከምንና ከምን?” “ከሰማይ በራሪ ከምድር ተሽከርካሪ…” “የሰማይ በራሪ፡፡”

አለቀ፡፡ ቡድን ተመሰረተ፡፡ ጨዋታው ሲያልቅ ቡድን አይኖርም፡፡ ምነው እንዲህ አይነቱን ‘የመንደር ልጅነት’ና ‘የሰንበቴ ተጣጪነት’ የቡድን መመስረቻ ክራይቴሪያዎች የማይሆኑበት ዘመን በመጣልንማ! እናላችሁ…ለጨዋታው ብቻ የሚሆን መቧደን ያለበት ዘመን በመጣልን የምንልበት ዘመን ደርሰናል፡፡ በጎጥና በመንደር እየተቧደንን ሉሲ እንኳን “አሜሪካ ይቺን ታህል ዓመት ቆይቼ እስክመጣ እንዲሀ ሆነው ይጠበቁኝ!” ብላ ሳትታዘበን አትቀርም፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የዚህ አገር ኳስ አደጋገፍ ግራ እየገባን ነው፡፡ አለ አይደል…ስታዲየም ግጥም ብሎ ስለሞላ እኮ ሁሉም የኳስ አፍቃሪ ነው ማለት አይደለም፡፡ ‘ኳስ አፍቃሪ’ መሆን ማለት እኮ…አለ አይደል…በየስድስት ወሩ ሌሊት አሥራ አንድ ሰዓት ለትኬት መጋፋት ሳይሆን መንገድ ላይ በጨርቅ ኳስ የሚደረጉ ግጥሚያዎችን እንኳን የሚያይ አይነት ማለት ነው፡፡ ዋናው ጉዳዩ ከ‘ቡድኖች’ ጋር ሳይሆን ከእግር ኳስ ስፖርት ነው፡፡ ስሙኝማ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ዘንድሮ አብዛኞቻችን ኳስ አፍቃሪዎች ሳንሆን ‘የቡድን ደጋፊዎች’ ነን፡፡

የኳስ ዓለም በሁለትና በሦስት የእንግሊዝ ቡድኖች ላይ የተገደበ ሲሆን… የምር ያጠያይቃል፡፡ “የቀበሌያችን ልጆች…” “የከፍተኛችን ልጆች…” ምናምን እየተባለ እኮ ኳስ ለምን ክብ እንደሆነች ግራ የሚገባቸው ሁሉ ወጥተው ይደግፋሉ፡፡ እነዚህ ‘የቡድን ደጋፊዎች’ እንጂ ‘የኳስ አፍቃሪዎች’ አይደሉም፡፡ እናማ… በቡድን ስሜትና በኳስ ማፍቀር ስሜት የሚሰጡት ድጋፎች ይለዩልንማ! ዘንድሮማ…አንዳንዶች ‘ዘር መቆጣጠር’ን ኳስ ውስጥ ሊያመጡት ሲሞክሩ ማየት…አለ አይደል…የምር አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ በማለዳው ‘ሀይ’ ካልተባለ በኋላ መዘዝ ይመዛል፡፡ አደባባይ ቆሞ አበጀሁ ቢላችሁ ይህ ባለጊዜ ምን ትሉታላችሁ፣ የሚሏት ነገር አለች፡፡ የሰላም፣ የወንድማማችነት ተምሳሌት በሆነው የተቀደሰው የኳስ ሜዳ በቡድን ድጋፍ እየገቡ “አበጀሁ!” የሚሉ አሉ ይባላል፡፡

ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ‘ቦተሊካው’ም እንዲሁ ነው፡፡ ‘የቡድኖች’ አበዛዝ! ልክ ነዋ…“በፖለቲካ ድርጅቴ የመጣ በዓይኔ የመጣ…” የሚለውን አብዛኛውን “ለመሆኑ የፖለቲካ ድርጅትህ ምን አይነት የትምህርት ፖሊሲ አለው?” ብላችሁ ጠይቁትማ! መጀመሪያ… “በቃ፣ ትምህርት ቤቶች መክፈትና አስተማሪ መቅጠር ነዋ! ሌላ ምን ጣጣ አለው…” ሊላችሁ ይችላል፡፡ እና የፖተሊካ ድርጅት ካርድ የ‘ቡድን አባልነት’ን እንጂ በፖለቲካ ድርጅቱ ፖሊሲዎች (ፖሊሲዎች ካሉት) እንደማያሳይ ልብ ይባልልንማ! በጎሉ አግዳሚ አርባ ሜትር ያህል ሽቅብ የሄደችውን ኳስ “ይቺ ኳስ ጎል የምትሆነው መቼ ነው?” ሲባል “ጎሉ ሲያዛጋ…” ያለው ሰውም የቡድን ደጋፊ ነው፡፡ (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አልፎ፣ አልፎ አንዳንድ ስፖርት ጋዜጠኞቻችን የሚጠቀሙት አዘጋገብ ላይ…አለ አይደል…የማይመቹኝ ነገሮች አሉ፡፡

እንደው ዜናዎቹ፣ ትንተናዎቹ ምናምን ላይ የሆነ ወንፊት ቢጤ አበጁላቸውና ፍሬ ፍሬውን ለእኛ፣ ገለባ ገለባውን ለቅርጫት አድርጉልንማ! እግረ መንገዴን…የአገርና የዓለምን እግር ኳስ በደንብ የሚያውቅ — የኢንተርኔቱን ‘ከት ኤንድ ፔስት’ ማለቴ አይደለም! — አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ “ኢትዮዽያ ሦስተኛ አፍሪካ ዋንጫ በላች የሚባለው ፊክሺን ነው…” ብሎ ክርክር ሊገጥመው እንደሞከረ ሲነግረኝ ነበር፡፡) “የቡድንና የቡድን አባቶች” “ከምንና ከምን?” “ከሰማይ በራሪ ከምድር ተሽከርካሪ” “የሰማይ በራሪ…” በቃ አለቀ፡፡ የቡድን አባል ለመሆን ተጨማሪ ‘ክራይቴሪያ’ አያስፈልግም፡፡ ይቺን ስሙኝማ…የአሁኖቹ ሳይሆን የ‘በፊተኛዎቹ’ ቡናና ጊዮርጊስ ሲጫወቱ በግራ ጥላ ፎቅ የገባ አንድ ተመልካች ኳሷ በየትኛውም አቅጣጫ በሄደች ቁጥር ይዘላል፣ ይጮሀል…ምን አለፋችሁ… የሚሆነውን ያሳጣዋል፡፡ ከብዙ ደቂቃዎች በኋላ አጠገቡ ወዳለው ሰው ተጠግቶ ምን ብሎ ቢጠይቀው ጥሩ ነው… “ቡኒ ካናቴራ የለበሰው ቡድን ስም ማነው?” ሰውየውም “ቡና” ሲል ይመለስለታል፡፡ ሰውየው ዝላዩን ቀጠለ፡፡

ትንሽ ቆይቶ እንደገና ወደሰወዬው ተጠግቶ ምን ብሎ ይጠይቃል መሰላችሁ…“ቢጫ የለበሰው ቡድን ስሙ ማነው?” ሰውየው ብሽቅ ብሎ ምን ብሎ መለሰለት መሰላችሁ…“ጠጅ!” (በ‘እውነተኛ ታሪክነት’ ይመዝግብልንማ፡፡) ሰውየው ያው ዝላዩን ቀጠለ፡፡ እናላችሁ…እንዲህ አይነት ‘የኳስ አፍቃሪ’ም ‘የቡድን ደጋፊ’ም ሳይሆኑ እንደ ጭቃ ሹም የሚቃጣቸው አሉ፡፡ ስሙኝማ…እግረ መንገዴን…ስለ ‘ቡድን ደጋፊነት’ ስናወራ ምን ይታየኛል መሰላችሁ…“ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ አትሞትም” የሚለው አባባል፡፡ እንደምናወራው ሰው ‘ዲ.ኤን.ኤ.’ የ‘ቡድን ድጋፋችን’ ከአየሩ ጋር የምናዛምድ መአት ነን፡፡ የለየለት ቅሽምናው ያለው ደግሞ እኛ ዘንድ ነው፡፡ እናማ…አስቸጋሪ ጊዜ ላይ ነን፡፡

ልቤ ተሸበረ ከሩቅ ስትጣሪ ሰማሁሽ አገሬ ስንቱን ብሶት ላውራሽ እናቴ ዘርዝሬ፣ ይሉ ነበር፡፡ እናማ…የቡድናዊ አመለካከት ብሶታችንን እያበዛው ነው፡፡ ከበቂ በላይ ብሶቶች የሌሉን ይመስል የዚህ አይነት ‘ፕሪሚቲቭ’ አስተሳሰብ…‘የሰሞኑ አጄንዳ’ ሲሆን ያሳዝናል፡፡ ‘ዘ ሳይለንት ማጆሪቲ’ ዝም ማለቱ አለማወቅ ሳይሆን ነገርዬው… ሽምብራውን ዘርተን እሸቱን ስንበላ አወይ የእኛ ነገር ሁልጊዜ ጥርጨጠራ ሆኖበት ነው፡፡ የሚያምነን ጠፋ፣ የምናምነው ጠፋ! “የቡድንና የቡድን አባቶች…” መባባል በጎጥ፣ በወንዝ ልጅነት፣ በ‘ጠበል ጠዲቅ’ ተጣጪነት…ምናምን የማይሆንበትን ዘመን ያፍጥልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል

ወንዶች ከፍቅረኛቸውና ከትዳራቸው ውጭ እየሄዱ እንዳመጣላቸው ለመተኛት ብዙም ምክንያት አያስፈልጋቸውም ይባላል። ኮስሞፖሊታን ረቡዕ እለት ያሰራጨው ፅሁፍ ግን፣ ከፍቅረኛ ጀርባ ማማተርና ግራ ቀኝ መቀላወጥ፣ በወንዶችም ሆነ በሴቶች ዘንድ እኩል ነው ይላል። ምናልባት በወንዶችና በሴቶች መካከል ልዩነት ካለ፣ የሚቀላውጡበት ምክንያት ላይ ነው። በእርግጥ፣ በመካከላቸው ልብን የሚያጠግብ ፍቅር ሳይኖር “ፍቅረኞች” የሚል ስያሜ ከያዙ፣ በስሜት ውጭ ውጭውን ለመናፈቅ ሌላ ምክንያት አያስፈልጋቸውም - አላፊ አግዳሚውን ለማየት አይናቸው የሚቅበዘበዘው ስለማይዋደዱ ነው። በፍቅር የሚዋደዱ ከሆነስ? ይሄ ነው ጥያቄው። ከፍቅረኛቸው ውጭ ሌላ ወንድ እንዲመኙ የሚገፋፉ

5 ምክንያቶች በሚል ኮስሞፖሊታን ባቀረበው ፅሁፍ መነሻነት ነገሩን ብናስብበት አይከፋም።

1. በኑሮ ሽግግር የሚፈጠር ጭንቀት የኑሮ ሽግግር ማለት፣ ከዩኒቨርስቲ መመረቅ ወይም ቀለበት ማሰር ሊሆን ይችላል። 30ኛ አመት እድሜ ላይ መድረስ፣ አልያም አንዱን ስራ ትቶ ሌላ ለመሞከር መወሰንም እንደ ኑሮ ሽግግር ይቆጠራል። የኑሮ ሽግግር፣ አነሰም በዛ፣ በአእምሮዋ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎችን መፍጠሩ አይቀርም። የህይወቴ አቅጣጫ ወዴት ያመራል? ከዚህ በኋላ ምንድነው የማደርገው?... እነዚህንና ሌሎች ጥያቄዎችን እያነሳች ከፍቅረኛዋ ጋር ብትመክር ተገቢ ነው፣ በጣም ከተደጋገመ ግን መሰላቸትን ያስከትላል። ለነገሩማ፣ ለብቻዋ ሆና ነገሩን እያወጣች እያወረደች ማሰብና ማሰላሰል እንዳለባት አያከራክርም። ለጥያቄዎቿና ለሃሳቦቿ፣ መቋጫ እያበጀች ካልሄደችና ያንኑን መልሳ መላልሳ የምታሰላስል ከሆነ ግን፣ አላስፈላጊ ጭንቀት ይፈጥርባታል። በማያቋርጥ የእንጥልጥል ስሜት እየተብሰለሰለች ምቾት ታጣለች። ይሄኔ፣ ከጭንቀት የሚገላግልና ለአፍታም ቢሆን ከአስቀያሚው ስሜት የሚያዘናጋት ሰው ብታገኝ ትመኛለች። ከፍቅረኛዋ ውጭ ሰው ፍለጋ ትማትራለች። (በእርግጥ፣ ሰው ማየት አስጠልቷት የምትተኛ ሴትም አትጠፋም። ወይም ከሴት ጓደኞቿ ጋር ሌላ ሌላ ነገር እያወራች ጭንቀቷን ለመርሳት የምትሞክርም ትኖራለች)። ነገር ግን፣ ከኑሮ ሽግግር ጋር የሚከሰት ጭንቀት፣ ከሌላ ወንድ ጋር እንድትወጣም ሊገፋፋት ይችላል።

2. የጓጓችለትና የኮራችበት ነገር፣ ፍቅረኛዋ ካልተጋራት ሴቶች፣ አድናቆትን መስማት ይፈልጋሉ ይባላል። በአድናቆት ጥምና ረሃብ ነጋ ጠባ ይሰቃያሉ ማለት ግን አይደለም። በጣም የምትወዱትን ነገር ሌሎች ሰዎች ቸል ሲሉት፣ የምትጓጉለትን ነገር ሲዘነጉት፣ የምታከብሩትን ነገር ከምንም ሳይቆጥሩት ሲቀሩ ምን ይሰማችኋል? ይደምቃል፣ ይሟሟቃል ያላችሁትን ነገር፣ ሰዎች ሲያደበዝዙትና ሲያቀዘቅዙት… ንዴት፣ ሃዘን፣ ድብርት ይፈጠር የለ? ቢያንስ ቢያንስ፣ “ኩም አልኩ” የሚባለው አይነት አስቀያሚ ስሜት ይፈጠራል። ሴቶች፣ ከምር ትልቅ ዋጋ የሚሰጡትና የሚኮሩበት ነገር ሲሰሩ፣ ስሜታቸውን ተጋርቶ ነገሩን እንዲያደምቅና እንዲያሟሙቅ የሚጠብቁት ፍቅረኛቸውን ነው። ፍቅረኛዋ፣ ነገሩን በቸልታ ካለፈው፣ “ኩም” ትላለች። ብሩህ አድርጋ የቀረፀችው የህይወት ምስል ይጨልምባታል። እናም የጨለመውን የሚያበራ፣ አልያም በመጠኑ ፈካ የሚያደርግ ሌላ ሰው ለማግኘት ግራ ቀኝ ትቃኛለች። በእርግጥ፣ ድብርትን የሚያባርርና ብሩህ ስሜትን የሚያላብስ ፊልም በማየት ከጭጋጋማው መንፈስ ለመላቀቅ የምትሞክርም ትኖራለች። አልያም ድብረቷ በጭፈራ እንዲወጣላት ከጓደኞቿ ጋር ናይት ክለቦችን ስታዳርስ ብታድር አይገርምም። የደበዘዘውን አለም የሚያበራ የሆነ ወንድ ለማግኘት እንድታስብም ሊያነሳሳት ይችላል።

3. ሊበጠስ የተቃረበ ግንኙነት እየሳሳ ሊበጠስ የደረሰ የፍቅር ግንኙነት፣ ምንም ቢሆን የፍቅረኞቹን ስሜት መረበሹ አይቀርም። በእርግጥ፣ “አንድ ሐሙስ የቀረው የፍቅር ግንኙነት”፣ አንዳንድ ሴቶችን ወደ ፍቅረኛቸው ይበልጥ እንዲጠጉ ሊገፋፋቸው ይችላል። ነገር ግን፣ ከወዲሁ ከፍቅረኛቸው ጀርባ አሻግረው እንዲመለከቱና ወደ ሌላ ወንድ እጃቸውን እንዲዘረጉ ሊያነሳሳቸውም ይችላል። የፍቅር ግንኙነት ከተቋረጠ፣ አንዳች የጉድለትና የክፍተት አስቀያሚ ስሜት ይፈጠራል። በዚህ ስሜት ላለመዘፈቅ ብላ ቅድመ ዝግጅት ታደርጋለች፤ ጉድለትን የሚሞላ ማካካሻና ምትክ ፍለጋ አካባቢዋን ትቃኛለች። ይሆናል የምትለው ወንድ ያየች ሲመስላትም፣ ለመሞከር ትነሳሳለች።

4. ሲጀመር አዝናኝ የነበረው ፍቅር ሲደነዝዝ በፍቅር ሲቀራረቡ፣ የሌት ተቀን ሃሳባቸው ሁሉ ደግ ደጉ ላይ ያተኩራል። አንዱ ከሌላው ለሚያገኘው ደስታ ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ። አንዱ የሌላውን መልካም ነገር ከልብ እያደነቀ ይረካል። ሲተያዩ፣ ሲያወሩ፣ ሲበሉም ሆነ ሲተኙ… ብዙ የሚያስደስቱ ነገሮችን ያገኛሉ። የልባቸውን ያወራሉ፣ ይቀላለዳሉ፣ ይተሳሰባሉ፣ ይከባበራሉ። በጣም ሲቀራረቡ ግን፣ ቀናት ተንከባልለው ወራት ሲያልፉ ግን፣ መከባበር ይቀርና መቆጣጠር በቦታው ይተካል። መቀላለድ ይቀርና መናቆር ይመጣል። የልብ ማውራት ሳይሆን ድብብቆሽና ጥርጣሬ ይበቅላል። ይሄ ሁሉ የሚሆነው፣ የአንዳቸውም ፍቅር ሳይቀንስ ነው። አንዳቸውም ሌላውን አልበደሉ ይሆናል። ግን፣ እርስ በርስ ፍቅራቸውን የሚያጣጥሙበትና የሚገልፁበት ሁኔታ ተለውጧል። ያንን የፍቅር አኗኗር ትተው፣ በሌላ “ልማዳዊ” አኗኗር ቀይረውታል። አንዱ ሌላውን የሚያይበት መነፅር ተለውጧል። ጥሩ ጥሩው ሳይሆን ጉድለት ጉድለቱ ብቻ እንዲታያቸው ማድረግ ጀምረዋል። ይሄኔ፣ የፍቅር ህይወታቸውን መልሰው ለማደስ መፍትሄ ካልፈጠሩ በቀር፣ አልያም የደነዘዘውን ሕይወት እንደእጣ ፈንታ በፀጋ ካልተቀበሉ በቀር፣ ደጅ ደጁን፣ ወጪ ወራጁን መመልከት መጀመራቸው አይቀርም።

5. አዳራቸው እንደ ቀድሞው አጓጊነቱ ሲያቆም ሲጀመር የነበረው ፍቅር ሲደበዝዝ፣ የአልጋ ቆይታቸውም እንደ ድሮው አጓጊነቱ እየቀረ ሲሄድ፣ መፍትሄ ያስፈልገዋል - ፍቅራቸውን ለማንቃትና ለማደስ፣ አልጋቸውን ለማነቃነቅና ለመፈንደቅ። ይሄ ቀላል አይደለም። በፍቅር ወይም በትዳር አንድ አመት ከቆዩ በኋላ፣ ግንኙነታቸው እንደ አጀማመራቸው አጓጊ እንዲሆን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያምኑበታል? ድሮ እሷ እሱን፣ እሱ ደግሞ እሷን ለመማረክ ነበር የሚያስቡትና የሚጥሩት። ከአመት በኋላ ግን ሃሳብና ጥረታቸው፣ አንዱ ሌላውን ለመቆጣጠር ነው - እንከን ፍለጋ። ይህንን ወደ ቀድሞው ትክክለኛ የፍቅር ግንኙነት መመለስ እንዳለባቸው ያምኑበታል? ካላመኑበት፣ የደነዘዘውን ፍቅር ማንቃትና የቀዘቀዘውን መኝታ ቤት ማሞቅ አይችሉም። ይሄኔ፣ ፍንደቃ እየናፈቃቸው ሌላ ወንድ ማሰብ የሚጀምሩና ወዲህ ወዲያ ጎራ የሚሉ ይኖራሉ።

Published in ባህል

“A thunderous applause” ሲል ይገልፀዋል አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ማርክ ሪቻርድሰን - በዚያች ቅፅበት በአዳራሹ ውስጥ የተሰማውን እንደ ነጐድጓድ የሚያስተጋባ የአድናቆት ጭብጨባ፡፡ እርግጥም ከአዳራሹ ጣራ ስር የተሰማው የጭብጨባ ድምጽ፣ ከአትላንታ ሰማይ ስር ከሚያስተጋባው የመብረቅ ነጐድጓድ በላይ ጐልቶ የመሰማት ሃይል አለው፡፡ የሚያባራ የማይመስል ዶፍ ከውጭ ፣ የሚያባራ የማይመስል ጭብጨባ ከውስጥ መዝነባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ያሳለፍነው እሁድ ረፋድ ላይ፡፡ አትላንታ፣ ጆርጅያ… ታዋቂው ሞርሃውስ ኮሌጅ ቅጽር ግቢ፡፡ የኮሌጁ የተማሪዎች መመረቂያ አዳራሽ የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች፣ የኮሌጁ የቀድሞ ተማሪዎች፣ መምህራንና ተመራቂ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ10ሺህ በላይ በሚሆኑ እንግዶች ተሞልቷል፡፡ ኮሌጁ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያስተማራቸውን የ2013 ተመራቂ ተማሪዎቹን መርቆ የሚሸኝበት አመታዊ ደማቅ በአል ዛሬ ነው፡፡

ይህ በአል ከአመት አመት በደማቅ ሁኔታ የሚዘጋጅ ቢሆንም፣ የዘንድሮው ግን የተለየ ነው። በበአሉ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት እንዲያስተላልፉና ንግግር እንዲያደርጉ የተመረጡት ክቡር ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ መሆናቸው በዓሉን ለየት ያደርገዋል፡፡ ለኮሌጁ 129ኛው የተማሪዎች ምረቃ ንግግር ለማድረግ የተመረጡት የእለቱ የክብር እንግዳ ፕሬዚዳት ኦባማ ከዚህ ቀደም በኮሌጁ የክብር ዶክትሬት ተሸልመዋል፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ስመጥር የጥቁሮች መብት ታጋዮችን ያፈራው ሞርሃውስ ኮሌጅ፤ የመጀመሪያውን ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን 129ኛው የኮሌጁ ተማሪዎች ምረቃ የክብር እንግዳ አድርጐ ለንግግር ሲጋብዝ፣ በንግግራቸው ውስጥ ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ‘ጥቁር የቀለም ቀንድ’ የሚሉት ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ አይደለም፡፡ የሆነው ሁሉ የሆነው፣ ‘ጥቁሩ የቀለም ቀንድ’ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ከወጣ በኋላ ነው፡፡

ተመራቂው፤ በሺህዎች ከሚቆጠሩ የዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል ተመርጦ ወደዚህ ከፍ ያለ መድረክ የወጣው በዕጣ አይደለም፡፡ ኮሌጁ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡና ተስፋ የሚጣልባቸው ብሎ ያመነባቸው ምርጥ ተማሪዎች ናቸው ወደ መድረኩ ወጥተው የስንብት ቃላቸውን ለተቀረው ተማሪና ለታዳሚው የሚያሰሙት፡፡ ‘ጥቁሩ የቀለም ቀንድ’ም ለዚህ ክብር የተጠራውና ወደ መድረክ የወጣው ከሌሎች በልጦ በመገኘቱ ነው፡፡ የኮምፒውተር ሳይንስ ተመራቂውና 3 ነጥብ 99 የመመረቂያ ውጤት ያለው ይህ ‘የቀለም ቀንድ’ ኢትዮጵያዊ በፀጋው ታደለ ይባላል፡፡ በክብር ታጅቦ ወደ መድረኩ የወጣው በፀጋው፣ ከ10ሺህ በላይ በሚሆነው የአዳራሹ ታዳሚ ፊት ቆሞ ያሰማው አጭር ንግግር በረጅም ጭብጨባ ነበር የታጀበው፡፡ ንግግሩን ያደመጡ ሁሉ ስለ ብስለቱ ተደነቁ፡፡ “እርግጠኛ ሆኜ ልንገራችሁ፡፡ ‘የማይቻል’ ብሎ ነገር የለም፡፡ ‘ተአምር’ የሚባል ነገር የለም። ‘የማይሳካ’ ብሎ ነገር በፍፁም አልተፈጠረም፡፡

ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ተስፋ ለማድረግ ድፍረት ሲኖራችሁ ብቻ ነው” ሲል በልበ ሙሉነት ተናገረ-በፀጋው፡፡ ይህን ንግግርና ንግግሩን ተከትሎ በአዳራሹ ውስጥ ማስተጋባት የጀመረውን ድምጽ ነው፣ አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ማርክ ሪቻርድሰን፣ “A great speech that received a thunderous applause!” በማለት የገለፀው፡፡ የባራክ ኦባማን አርአያነት ያወሳውና በመላ ታዳሚው ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው የበፀጋው ንግግር፣ የዕለቱን የክብር እንግዳ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ግን በተለየ ሁኔታ ነበር የነካቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የበፀጋው አባባል፣ ኦባማ በ2006 ለንባብ ካበቁት “The Audacity of Hope” የተሰኘ መፅሐፍ የተወሰደ ነበር፡፡ እርግጥ ኦባማ የተመራቂውን ንግግር ያደነቁት ከእሳቸው መፅሐፍ ስለጠቀሰና የአድናቆት ቃል ስለ ሰነዘረላቸው አይደለም፡፡ በንግግሩ ውስጥ ያነሳው ፍሬ ነገርና ቁርጠኛ የለውጥ ዝግጁነቱ ነው በውስጣቸው ዘልቆ ያስደመማቸው፡፡ ኦባማ ውስጥ ውስጡን ተደመው ዝም አላሉም። ተራቸው ደርሶ ለንግግር ወደ መድረክ ሲወጡ በፀጋውንና ንግግሩን በልባቸው ይዘው ነው፡፡

በሞርሃውስ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጆን ዊልሰን ጋባዥነት ለንግግር ወደ መድረኩ የወጡት ኦባማ፣ ጊዜ ወስደው ለመላው ተመራቂ ያዘጋጁትን መደበኛ ንግግር የጀመሩት ወደ አንድ ተመራቂ ባነጣጠረ ለዛ ያለው አድናቆት ነው፡፡ “እርግጥ ከእኔ በፊት ንግግር ካደረገው ሰው በኋላ ንግግር ለማድረግ መምጣት አስቸጋሪ ነው” ብለው ጀመሩ ኦባማ፤ የተናጋሪውን አንደበተ ርዕቱነት በሚያደንቅ አነጋገር፡፡ “ይቅርታ … ዶክተር ዊልሰንን ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ የሚያስቅ ስም ያለውን የቅድሙን ከሲታ ልጅ ማለቴ ነው … ቢሲጋው ታድሌ፡፡ ይህ ልጅ ወደፊት የሆነ ትልቅ ነገር እንደሚሰራ ይሰማኛል” በማለትም ለተመራቂ ተማሪዎች ያዘጋጁትን ሰፊ ዲስኩር ማሰማታቸውን ቀጠሉ፡፡ በፀጋው ታደለ ትልቅ ነገር ይሰራል ተብሎ ተስፋ የሚጣልበት ባለ ብሩህ አእምሮ ወጣት ስለመሆኑ በልበ ሙሉነት የተናገሩት ኦባማ ብቻ አይደሉም፡፡ ‘ሲ ኤን ኤን’ን ጨምሮ ስለ ዕለቱ የምረቃ ስነ ስርአት ዘገባ ያቀረቡ በርካታ የአሜሪካ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ስለ በፀጋው ታደለ እና በኦባማ ስለተቸረው አድናቆት ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ በርካታ ድረገፆችም ይህን ኢትዮ አሜሪካዊ ‘የቀለም ቀንድ’ በተመለከተ በምስልና በቪዲዮ የታገዘ መረጃ ይፋ ማድረግ ይዘዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ነዋሪነቱ በአትላንታ ጂዩርጂያ የሆነው በፀጋው ታደለ፣ ትውልድና እድገቱ በአዲስ አበባ መሆኑንና የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት መከታተሉን፣ ወደ አሜሪካ አቅንቶ በኒውጀርሲ ሲቲ “ኤል ሲሲ ኤስ ሲ” የተባለ ት/ቤትና በሞርሃውስ ኮሌጅ መማሩን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ወጣት በተመረቀበት የኮምፒውተር ሳይንስ ሙያ በታዋቂው የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ ውስጥ ሰፋፊ ስራዎችን ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ማርክ ሪቻርድሰን “በፀጋው ታደለ፣ የወደፊቱ የአለም መሪ” በሚል ርዕስ ሰሞኑን በፃፈው ዘገባ ጠቁሟል፡፡ ማርክ ሪቻርድሰን ስለ ወጣቱ የሰጠውን አስተያየት እነሆ ብለን እናብቃ፡፡ “ይህ የክብር ተመራቂ ሌላ ክብርም ተጐናፅፏል። የተከበሩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ንግግር ባደረጉበት መድረክ ላይ ቆመው የመናገር ዕድል ካገኙ ጥቂት ሰዎች አንዱ ነውና!”

Published in ህብረተሰብ
Monday, 27 May 2013 14:10

ትርፍ ጣት

ደሴ፡፡ በቀን ሃያ ሰባት፣ በዕለተ ሰንበት - እሁድ፣ በባለ አንድ አጥንቱ…ጥቅምት ወር ውስጥ፣ ባለፈው ሚሊኒየም፣ በ1990ዎቹ መጀመሪያ … መሆኑ ነው፡፡ ልክ ከንጋቱ 12፡10 ይላል… ሌሊት ቢመስልም፡፡ የደሴ ፒያሳ በህዝበ ክርስቲያን እየተጨናነቀች ነው፡፡ የመድሐኒዓለምን ቤተክርስቲያን ለመሳለም ህዝብ አዳም ይርመሰመሳል፡፡ ጉም ቢጤ ሰማዩን ስላለበሰው አካባቢው ያህያ ሆድ መስሏል፡፡ በቀዝቃዛ ድባብ ተሸብቧል፡፡ ከወትሮው አጥንት እየቆረጠሙ ካልሆነ በቀር እንዲህ በቀላሉ ሊቋቋሙት የማይችሉት የጥቅምት ውርጭ ፊት ያቃጥላል - አብዛኛው ምዕመን ልብስ ደራርቦ ነው በዚህ ሰዓት እየተንቀሳቀሰ ያለው… ከቴሌ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ለልመና የተቀመጠው ህፃን ‹‹ሞት ባይኖር››፣ የጥቅምት ብርድ በርሃብ የተጐዳ አካሉን ያንዘረዝረዋል።

እነዛ ትናንሽ ጥርሦቹ እርስ በርስ ይገጫጫሉ፡፡ የተቀመጠበት አስፋልት ቅዝቃዜው፣ ሽባ እግሮቹን በድን አድርጓቸዋል፡፡ ጣቶቹ በፍርሃትና በጥቅምት ቆፈን ተኮርኩደዋል… “ስለ መዳንአለም … እማማዬ፣ አበባዬ አትለፉኝ…የአይኔ ብልሃኔ የፈሰሰ…” ኮልታፋ አንደበቱ ከሚያንሰፈስፈው ብርድ ጋር አብሮ አሳዛኝ ድምፀት ያሰማል፡፡ “እማማዬ… እልቦኛል … ስለ መዳናለም ብለው …አይነ የለለኝ…” እያለ አይነስውሩ ህፃን በመከራ እንዲያጠናው የተደረገውን የልመና ዜማ ያዥጐደጉደዋል፡፡ “እኔ ልንሰፍሰፍ የኔ ልጅ!... በዚህ ውርጭ በሚፈላበት ሰዓት እራቁትህን ጥላህ የሄደችው እናትህ ትሆን? ኧረ እቺ እናት አይደለችም…” አሉ አንዲት ቤተክርስቲያን ሳሚ 25 ሳንቲም እየሰጡት።

ህፃን ሞት ባይኖር፣ በዚህ ውርጭ እንደዚህ መንጋጋና መንጋጋው እየተንገጫገጩ፣ ጥቁር ፊቱ በውርጭ ደብኖ፣ እጅና እግሩ ተኮማትረው…ሲያዩት እኚህ ምስኪን እንስት የሚያደርጉት ጠፋቸው፡፡ ድህነት ቤቱን የሠራባቸው እናት ባይሆኑ አንስተው ይዘውት ቢሄዱ በወደዱ… “እማማዬ …ስለ መድሐናለም…አትለፉኝ… እግሌ የማይሄድ…” “ወይ…እኔን!...አይ አንተ እግዜር ለእኛ መማሪያ ብለህ አይደል ይህን ነፍስ የማያውቅ አንድ ፍሬ ህፃን እንዲህ አድርገህ ማሳየትህ!... አይዞህ የኔ ልጅ… መቼ ታዲያ እኛ እንማራለን…” እያሉ ሌላዋ ቤተክርስቲያን ሳሚ አጉተመተሙ፡፡ ልባቸው በሀዘን ተወግቷል፡፡ ወዲያው ከወደ ጉያቸው እጃቸውን ከተው ሳንቲም የተቋጠረበት እራፊ ጨርቅ አወጡና 10 ሳንቲም ሰጥተውት ሄዱ… እናታዊ ፍቅር የተላበሰው የሴትዮዋ ንግግር፣ የሞት ባይኖርን ትንሽ ልብ በትዝታ አቀለጠው፡፡ ለተወሰኑ የደቂቃዎች ክፍልፋይ የልመና መዝሙሩን መቀኘት አቆመ፡፡ ሞት ባይኖር በሃሳብ ጭልጥ ብሏል... በህፃን የልቡ ጽላት ተቀርፆ የቀረው የበፊት ህይወቱ በዐይነ ህሊናው ይታየው ጀመረ… ሁሉንም ነገር እያስታወሰች ያች ትንሽ ልቡ በትዝታ ተጠበሰች…                                      * * *

የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ወላጆቹ፣ በሙሽርነት ጊዜያቸው የተቀበሉት የፍቅራቸው ማጣፈጫ ገፀ - በረከታቸው ከመኖሪያ ግቢያቸው ጠፋ፡፡ ብስራት፣ ልጇ ወደ ጐረቤት የሄደ መስሏት፣ ለወዲያው ብዙም አልደነገጠችም፤ መፈለጓን ግን አላቋረጠችም። የዛን ጊዜው አላዛር ግን መሰወሩ ቁርጥ ሆነ፡፡ አባቱ ማቲያስ የሚሾፍራትን መኪና እየነዳ ተናፋቂ ገፀበረከቱንና ተወዳጅ ሚስቱን ለማየት… ምሳውንም ለመብላት በጉጉት ሲመጣ፣ የልጁ መጥፋት መርዶ ተነገረው፡፡ ማቲያስ ክው ብሎ ቀረ፡፡ በህይወት ዘመኑ እንደ ዛሬ ደንግጦ አያውቅም... ህፃን አላዛር ድንቡሼ እንቦቀቅላ ነው፡፡ በቀሰም የተነፋ ፊኛ የሚመስሉት ጉንጮቹ፣ በሽፋሽፍቶቹ ውስጥ ተደብቀው በራሳቸው ምህዋር እየተላወሱ እንደ ፈርጥ የሚያበሩት ዐይኖቹ፣ በሥርዓት የተሰደሩት ትናንሽ ጥርሶቹ፣ ሣቅ ሲል ትምብክ ከሚሉት የጉንጮቹ ስርጉዶች ጋር ተዳምረው አላዛርን የሚያሳሳ፣ አጓጊ ህፃን አድርገውታል፡፡ አለባበሱ እና ሰውነቱ በቅንጦት የሚያድግ የበኩር ልጅነቱን ያንፀባርቃሉ፡፡ በተለይም ሲወለድ ጀምሮ ከቀኝ እጁ ትንሽ ጣት ጐን በኩል የበቀለችው ትርፍ ጣቱ፣ እግዚአብሔር በተለየ መንገድ ፈጥሮ ያበረከተላቸው ስጦታ እንደሆነ አድርገው ወላጆቹ እንዲቆጥሩት አድርጋዋለች፡፡ አላዛር ከቤቱ ግቢ ተሰርቆ ከመወሰዱ በፊት የተገዛችለትን የላስቲክ ኳስ እያንከባለለ ነበር፡፡ እሱ ሲሰወር የመጫወቻ ኳሱ ግን አጥሩን ተጠግታ አላዛርን በጉጉት ትጠባበቃለች፡፡ የትላንቱ አላዛር፣ የዛሬው ሞት ባይኖር ከቤቱ ሲጠፋ የ3 ዓመት ተኩል ልጅ ነበር፡፡

* * *

የዛሬ ዓመት አንድ ሰው በለሆሳስ ወደነ ማቲያስ ግቢ ተጠጋ፡፡ አካባቢውን በጥልቀት ቃኘ፡፡ ከአላዛር በቀር ማንም ሰው በግቢው አይታይም፡፡ ወደበሩ ተጠጋና ትንሹን እንቦቃቅላ በንስር ዓይኑ ዘገነው፡፡ “ማሙሽዬ…ና…እንካ ከረሜላ” “እ…የታል?...ትሰጠኛለህ?” “አዎ! እንካ ማሙሽዬ…እንካ ይኸው…” የተጠቀለለ ከረሜላ እያሳየ ከግቢው አስወጣው። የተወሰነ መንገድ እጁን ይዞ ከወሰደው በኋላ በሚገርም ፍጥነት በጋቢው አፍኖ ይዞት ተፈተለከ፡፡ ማንም አላየውም፤ ቢያየውም ማንም አያውቀውም - ሻምበል እርገጤን፡፡ ሻምበል እርገጤ በደርግ ዘመነ መንግስት በሰሜን ጐንደር ክፍለ ሀገር፣ በአዘዞ ከተማ በአራተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ባለስልጣን ነበረ፡፡ የደርግ መንግስት ሲገረሰስ ለጊዜው ከአካባቢው ቢሰወርም፣ በእርገጤ ጥይት አንድ ወንድሙን ያጣው ማቲያስ ግን ዱካውን አሽትቶ ደርሶበት ነበር… እጅ ከፍንጅም አስይዞታል። በግፍ ደም የታጠበው ሻምበል እርገጤ ወህኒ ይወርዳል፡፡ ለሰባት ዓመት እንደታሰረ አእምሮው ተነክቷል ተብሎ ይለቀቃል፡፡

ለብዙ ጊዜ በጐንደርና በአዘዞ ጐዳናዎች ልብሱን ቀዶ ሲንቀዋለል ከቆየ በኋላ፣ አድራሻው ሳይታወቅ ከቦታው ይጠፋል። እነሆ ዛሬ እራሱን ቀይሮ ለወራት ሲደክምበት የቆየውን እቅድ እውን ሊያደርግ የማቲያስን ልጅ ሰርቆ ከጐንደር ተሰውሯል፡፡ ብልጠትና ድፍረት በተላበሰ ቅልጥፍና አላዛርን ይዞ ከብዙ ድካምና እንግልት በኋላ የወሎን ምድር እረግጧል፡፡ ከዚያም፣ ከደሴ 210 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የሣይንት ወረዳን፣ የህፃን ሰቆቃና ግፍ ሊያሳየው መርጦታል… ሻምበል እርገጤ በጠፍ ጨረቃ አላዛርን ሽኮኮ አድርጐ የጓሜዳን ፀጥ ያለ ሜዳ ተያይዞታል፡፡ በለሊት ከአንድ መንደር ውስጥ ደረሰ፡፡ የእትብቱ መቀበሪያ በመሆኑ ቦታውን በሚገባ ያውቀዋል። የተዘጋውን የዘመዶቹን ቤት ከፍቶ ጨለማው ውስጥ ገባ፡፡ ባሻጋሪ ካለው ቤት እህቱን ጠርቶ ኩራዝ በራላቸው፡፡ አላዛር ለሳምንት ረሃብና ግርፋት እየተፈራረቀበት አይሆኑ ሆኖ ነው የደረሰው፡፡ በዚህ ጭር ባለ መንደር ሳምንት እንደነገሩ ቆዩ። ዛሬ ህፃኑ አላዛር ለማመን የሚያስቸግረውን የግፍ ፅዋ ሊያንጫልጠው ተደግሶለታል፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት ነው፡፡

ህፃን አላዛር ከመደበ ላይ አንቀላፍቷል፡፡ እርገጤ ወደ ውጭ ወጣ ብሎ የአጋም እሾህ ቆርጦ ገባ፡፡ ህፃኑ ከተኛበት አይኖቹን ከሽፋሽፍቶቻቸው መለቀቃቸው፡፡ ረሃብ ያደከመው ህፃን፣ በድንጋጤ ጮኸ፡፡ ወዲያው አንዳች ነገር አፉን ጥርቅም አድርጐ ዘጋው፡፡ ነፍሱ ግን እንደ ኢየሱስ፣ “አባት ሆይ…ይህንን ጽዋ ከኔ ውሰድ!...” እያለች በህፃንኛ ልሣን ትማፀን ነበረ... እርገጤ በአመጣው እሾህ በጭካኔ ሁለቱንም አይኖቹን በፍጥነት ወጋቸው፡፡ ህፃን አላዛር ተፈራገጠ፡፡ የህፃኑን አፍ በለበሰው ድሪቶ ታፍኗል። አላዛር የማይሰማውን ጮኸቱን ለቀቀው፡፡ በዚህ ጭር ባለ የባዕድ ሰፈር፣ በዚህ ፀጥ ባለ ጨለማ…ማን ሊደርስለት!? ደም፣ ከጓጐለ ውሃ መሳይ ፈሳሽ ነገር ጋር ተቀላቅሎ የከሰሙትን ጉንጮቹን እየገመሰ ጐረፈ፡፡ ከቀናት በኋላ አይነስውሩ ሞት ባይኖር ከአስከፊው ኑሮው ጋር ተጋፈጠ፡፡ በጠፋው አይኑ ብቻ አልተማረም፤ ማታ ማታ መላ አካላቱን በቅቤ እየታሸ በዘነዘና ከታች እስከ ላይ ይዳመጣል። የሚፈለገው ሽባ ሆኖ፣ በአካላቱ ላይ ለውጥ ሳይመጣ፣ ለብዙ ጊዜ እንዲኖር ማድረግ ነው።

ለመከራ የተፈጠረው ይህ ህፃን፣ አሁን ዐይኖቹ አያዩም፤ እግሮቹም አይራመዱም፤ ሽባ ሆነዋልም፡፡ የሰው ልጅ መከራን ሊቋቋም በተለየ መንገድ ተፈጥሮ እንዳዘጋጀችው በዚህ ህፃን የተረጋገጠ ይመስላል፡፡ ደሳሳዋ የቤተ - ሙከራ ጐጆ አላዛርን በሚገባ አሰልጥና ልብ የሚሰርቅ ጥሩ ለማኝ እንዲሆን አብቅታዋለች... አሁን ሞት ባይኖር ደሴ ፒያሳ፣ ቴሌ መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት ቁጭ ብሎ በሀሳብ የነጐደው፣ ይሄ ሁሉ የሕይወት እጣው ትዝ ብሎት ነው፡፡ እንደ ህልም… እናት አባቱም ትዝ ይሉታል፡፡ አሁን በጐኑ ቢያልፉ ግን አያያቸውም፡፡ ያቺ የሚወዳት የላስቲክ ኳሱ ብትመጣ እንኳ ሊያንከባልላት አይቻለውም፡፡ እግሮቹ ሽባ ሆነው ተሳስረዋልና፡፡ ልብ የሚሰርቀው ያ ኮልፋታ አንደበቱ፣ አይነስውርነቱንና ሽባነቱን አክሎ የአዳም ዘርን ልብ በሀዘን ያንበረክካል፤ እርገጤም የፈለገው ይሄን ነበር፡፡ በየቀኑ ብዙ ገንዘብ ያሳፍሰዋል፡፡ እንዲህ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመሆን እያገለገለ አንድም ቀን ግን ሆዱ እስኪጠግብ እንዲበላ አይፈቀድለትም፡፡ በአብዛኛው ለነፍሱ ማቆያ ሽርፍራፊ ዳቦ ቢጤ በውሃ ይቀርበለታል፡፡ ሆዱ እስኪጠግብ የሚያስፈልገውን ከበላ፣ ሰውነቱ ስለሚጠግብና ወዘናው ስለሚመለስ አያሳዝንም፤ የመጽዋችን ልብ በሀዘን አይሸነቁጥም። ስለዚህ ሁልጊዜ መራብ አለበት፡፡ መራብ፣ መጠማት…

* * *

አሁን እርገጤ ከሰኞ ገበያ በኩል ወደ ቴሌ በፍጥነት እያመራ ነው፡፡ ሞት ባይኖር የልመና ቅኝቱን ሲያዜም ስላልተሰማው፣ ተበሳጭቷል፡፡ ወደ ቦታው ሲደርስ በአራቱም አቅጣጫ አማተረና ወደ ሞት ባይኖር ተጠጋ፡፡ ድሪቶ መሳይ ጋቢውን እየሰበሰበ በርከክ አለ፡፡ “ሞት ባይኖር!” ድምፁን ዝቅ አድርጐ ተጣራ፡፡ “እ… አባዬ… ስለመዳናለም አባቶቼ…” በማለት ሞት ባይኖር መለመኑን ትቶ ዝም በማለቱ ሳቢያ፣ የሚደርስበትን መከራ ለማጠፋፋት በቅልጥፍና ወደ ልመናው ሊገባ ሞከረ፡፡ “እኔ ስመጣ ነው መለመን የምትጀምረው?...ቆይ!” አስፈራራው፡፡ ሞት ባይኖር ፀጉሩ አድጐ እንዲታይ አይፈልግም፤ ሁልጊዜ ይላጫል፡፡ ጥላሸት ከቅቤ ጋር እየተለወሰ ስለሚቀባ ጠይም ገላው ወደ ጥቁርነት ተለውጧል፡፡ ተፈጥሯዊ የመቆም ሃይላቸው ተሰልቦ የሚልፈሰፈሱት ሽባ እግሮቹ፣ እንደ ወጥ ማማሰያ ቀጥነው፣ ከአሥር ቦታ በተጣጣፈው ቁምጣው ሾልከው ሲታዩ ያሰቅቃሉ፡፡ ማንም ቢሆን ሞት ባይኖርን አይቶ አላዛር መሆኑን ማወቅ ቀርቶ መጠርጠር አይቻለውም፡፡ አላዛር ዛሬ ፍፁም አዲሱ ሞት ባይኖር ሆኗል፡፡ “አሁን እመለሳለሁ…በደንብ እየለመንክ ቆይ…እሺ?” እርገጤ ሃይል የታከለበት ቀጭን ወታደራዊ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ “እሺ! አባዬ…” ሞት ባይኖር ተነፈሰ፡፡ “በደንብ ዛሬ ከለመንክ…ዳቦ ይገዛልሃል… አዲስ ልብስም ይጨመርልሃል” በማለት ሀረር የቁልቢ ገብርኤል ክብረ በዓል ዕለት ብዙ ገንዘብ በመለመኑ የገዛለትን የሰልባጅ ቁምጣ፣ ማማሰያ እግሮቹን አጋልጣ ታሳይ ዘንድ ወደ ላይ ሰበሰባት፡፡ ሳንቲሞቹን ለቃቅሞም እንደልማዱ ተሰወረ - ሻምበል እርገጤ፡፡

ሞት ባይኖር በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ሳያቋርጥ የልመናውን ዜማ ያንበለብል ገባ፤ “እማምዬ፣ አባብዬ…ስለ መዳናለም ብሎ… እለዳት የለኝም… እማምዬ ይልጅነት ብልሃኔ ፈሷል… አባብዬ እዘኑልኝ…” ሞት ባይኖር ልሣኑ እስኪዘጋ ልመናውን ተያያዘው፡፡ ርሃብና ውሃ ጥምም ሲያሰቃየው ለተወሰነ ጊዜ ቢያርፍም፣ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለማክበር ያለ የሌለ ሃይሉን አሟጦ መለመኑን ይቀጥላል… አሁን ፒያሳ የሰው ዘር በብዛት ይታይበታል። ወደ መድሐኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ከሚያልፉ ከሚያገድሙ ሰዎች ውጭ ሌላውም ሽርጉድ ይላል፡፡ ዛሬ ማክሰኞ የሥራ ቀን በመሆኑ የመንግስት መኪኖች ከቴሌ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ተኮልኩለዋል፡፡ አንድ የመንግስት መኪና ሞተሩን ቀሰቀሰ። “እር…እር…” ካለ በኋላ ከቆመበት ተንቀሳቀሰ። ወደታች ለመታጠፍ ወደኋላ መሄድ ነበረበት። አሁን ወደኋላ እየሄደ ነው… ሃይሉን ጨመር አድርጐ ወደኋላ እየተጓዘ ነው... ከድምፁ ውጭ አቅጣጫውን የማይመለከተው ሞት ባይኖር ከሞት ጋር ተፋጧል፡፡ ድምፁ እየቀረበ ሲመጣበት ሊገጭ እንደሆነ ያወቀ ይመስል እጆቹን እያወራጨ ጮኸ… ከአካባቢው ያሉት ሰዎች ሁሉ ጮኹ፡፡ ሹፌሩ በደመነፍስ ፍሬን ሲይዝ ከኋላ ጐማዎቹ ሥር ሞት ባይኖር እስከለመናቸው ሳንቲሞቹ ድረስ ቁጭ ብሏል፡፡ በጣም በሚሰቀጥጥ ሁኔታ መኪናዋና ሞት ባይኖር ተፋጠው ታዩ፡፡ ሹፌሩ ፍሬን ይዞ እንደ ወረደ በአንድ ነገር እርግጠኛ ሆኗል፤ ከመኪናው የኋላ ጐማ ያጠፋውን ነፋስ ለማየት የስጋም የመንፈስም ጥንካሬ ያስፈልገዋል፡፡

እግሮቹ ተሳሰሩ፤ እንደምንም ብሎ እግሮቹን እየጐተተ ወደ መኪናው የኋላ ጐማ አመራ… መንገደኛው ግን በየአፉ ተቀባበለበት፡፡ “ምን ማለት ነው? አታይም? ለትንሽ እኮ ነው የተረፈው!?...” በማለት አምባረቁበት፡፡ “አንጐበርህ ሳይለቅህ ለምን ትነዳለህ!?” “ከዚህ ቦታ ሰው ይኖራል ብዬ አልገመትኩም… መድሐኒዓለም በዕለተ ቀኑ አወጣኝ!” እያለ ሹፌሩ መናገሩን እንጂ፣ በቅርብ ርቀት የመድሐኒዓለም ቤተ ክርስቲያን መኖሩን አላወቀም፡፡ በሁኔታው ተደናግጦ ስለነበረ ከኪሱ አንድ ብር አውጥቶ ወደ ሞት ባይኖር መቅረቡንም ልብ አላለም፡፡ የሰው ኮቴ ስትሰማ እየጮህክ ለምን የተባለው ሞት ባይኖር ከመቅጽበት፣ “አባብዬ፣ ስለ መዳናለም…” በማለት ልብ በሚሰርቅ ቅላፄ ሲማፀነው አንዳች ነገር ውስጡን ሰቀጠጠው፡፡ ለምን ልቡ እንደራደ፣ መንፈሱ እንደተረበሸ ባያውቀውም፣ ሹፌሩ አንዳች የሚያውቀው አይነት ቅላፄ የሰማ መስሎት ህዋሶቹ ሁሉ ነዘሩት... ሞት ባይኖር፣ “አባባዬ፣ ስለመዳናለም …” አለ፣ የጥቅምት ውርጭ የኮደኮዳቸውን ጣቶቹን አንቀርፍፎ፡፡ ሹፌሩ አንድ ብር ጠቅልሎ ሊሰጥ ሲል ከተዘረጋለት እጅ ላይ የተመለከታት “ትርፍ ጣት” ግን ከመንዘር አልፋ አወራጨችው … በህይወት ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ ክው ብሎ ደነገጠ፡፡

እራሱን ስቶ ከመውደቁ በፊት ለዓመታት ሳይጠራው የኖረው ቃል ካፉ ላይ ባረቀበት፡፡ “እንዴ! አላዛር! …ነህ?” በደመነፍስ ተጣራ - ሹፌሩ፡፡ “እ … አቤት! እም … ሞት ባይኖል …” አለ ህፃን አላዛር፤ ሞት ባይኖር አዲሱን ስሙን መናገር እንዳለበት የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ትዝ ብሎታል። በድንገት በሰማው ድምፅም ተረብሽዋል፡፡ ሹፌሩ፣ የሞት ባይኖርን የፈሰሱ አይኖች ጋርደው በፍጥነት የሚርገበገቡትን ሽፋሽፍቶቹን በጥልቀት ተመለከታቸው፡፡ ለማመን እስኪያቅት፣ መላ ሰውነቱ ተንዘፍዝፎ ወደቀ … በልሳን እንደሚያወራ አዲስ አማኝ አንደበቱ እየተኮላተፈ ተዘረረ፡፡ በድንገት የተገናኙት አባትና ልጅ በመንገደኛ ተከበቡ፡፡ ከፍተኛ ግርግር ተፈጥሯል፡፡ የትራፊክ ፖሊሲም በሁኔታው ተገርሞ ሹፌሩን ደግፎ አነሳው፤ “አላዛር … የኔ ልጅ አላዛር…” ሹፌሩ እንደማበድ አደረገው፤ እምባው በጉንጮቹ ይወርዳል፡፡ “እንዴ … ልጁ ነው? ልጁ ነው እንዴ!? ...” መንገደኛው የበለጠ ተጯጯኸ፡፡ “እ … አባዬ … አዎ!...አባዬ” አለ ሞት ባይኖር። ወዲያው የእርገጤን ድምፅ የሰማ መስሎት ያቺ ትንሽ ልቡ በፍርሃት እራደች፡፡

“ልጄ ነው! እባክህ ትራፊክ ተወኝ ልጄ ነው … ከሦስት ዓመት በፊት የጠፋው ልጄ …” ሲል ሁሉም ሰው እንደገና ደነገጠ … ቀልጣፋው ትራፊክ ሹፌሩን በፍጥነት በፊት ለፊት ወደሚገኘው የፖሊስ መምሪያ ወሰደው፡፡ የከበባቸውን መንገደኛ በተነ... በፖሊስ መምሪያ ጽህፈት ቤት አንዲት ጠባብ ቢሮ ውስጥ የፖሊስ መምሪያ አዛዡና ማቲያስ በተከፈተው መስኮት አሻግረው ሞት ባይኖርን እያዩ፣ የሚፈልገውን ሁሉ የመረጃ ልውውጥ አድርገዋል። በመቶ ሜትር ርቀት አካባቢ ሁሉ ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች በተጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡ ከቀኑ 6፡43 ይላል፡፡ ፀሐይ በደሴ ሰማይ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የወጣች እስክትመስል በሙቀቷ ትገሸራለች፡፡ ወበቅ ሲበዛባት ሞት ባይኖር ከሚለምንበት አስፋልት መንገድ ላይ ተዘረረ። ከፖሊስ መምሪያው አዛዥ ጋር ሆኖ በመስኮት እያጮለቀ የሚያየው ሹፌር አሁን ግን አላስቻለውም። እወጣለሁ እያለ እየታገለ ነው፡፡ “ፀሐዩ እኮ አቃጠለው! ሞተ’ኮ መቶ አለቃ!” “ተረጋጋ! ወንጀለኛው በምንም ታምር ሊያመልጥ አይገባም…” አለ ፖሊስ አዛዡ አይኑን በመስኮት አሾልኮ ሞት ባይኖር ላይ እየተከለ፡፡ “መቶ አለቃ ይሄ ልጅ ከሞተ…” “አይሞትም … ምነካህ? … እሺ ልጅህን እንደዚህ ያደረገው፣ ኑሮህን የበተነው ወንጀለኛ መያዝ የለበትም ነው የምትለው!? … ባክህ ተረጋጋ!›› አለ የፖሊስ አዛዡ ትንሽ ቆጣ ብሎ፡፡ አሁን 7፡05 ይላል፡፡

ከወደ ሰኞ ገበያ አካባቢ ሁለት ሰዎች ወደ ፒያሳ እየመጡ ነው፡፡ አንዱ ወደ “ከበደ አበጋዝ ሆቴል” ሲያቀና፣ ሌላኛው ወደ መድሐኒዓለም ቤተክርስቲያን አቅጣጫ ገሰገሰ፡፡ ያደፈ ጋቢ ያደረገው ገበሬ መሳዩ ሰው፣ ወደ ሞት ባይኖር አቅጣጫ እያመራ ነው፡፡ ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች በቅርብ እርቀት እየተከታተሉት ነው። ጋቢውን ወደ ትከሻው አጣፋ፡፡ እርገጤ ምን እንዳለው ባንሰማውም፣ ሞት ባይኖር ደንግጦ ለመነሳት ሞከረ፡፡ ግን አልቻለም፡፡ ወደ አስፋልቱ ድፍት አለ፡፡ የአላዛርን ሁኔታ እያየ ያለው ማቲያስ፣ አሁን ምን እየተሰማው እንደሆነ በቃላት መግለፅ ይከብዳል ... እርገጤ በአራቱም አቅጣጫ ገልመጥ ገልመጥ አደረገና ጐንበስ ብሎ የተመፀወቱ ሳንቲሞችን ለቃቅሞ፣ ከኮቱ ኪስ ጨመራቸው፡፡ ለሳንቲም ማስቀመጫ ያነጠፈውን ጨርቅ አጣጥፎ ከኪሱ ከተተው፡፡ ወዲያው ሞት ባይኖርን አንድ እጁን አንጠልጥሎ አነሳውና ሽኮኮ አደረገው፡፡ ፈጠን ፈጠን እያለ እየተራመደም ወደ መጣበት ወደ ሰኞ ገበያ አቅጣጫ ተጓዘ፡፡ ግን ብዙ አልራቀም፡፡ “ቁም!” አለ አንድ ትግስቱ ያለቀ ፖሊስ፡፡ ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች ሻምበል እርገጤን በቁጥጥር ስር አዋሉት፡፡ ሹፌሩ ማቲያስ ለሁለተኛ ጊዜ ሻምበል እርገጤን ለህግ አሳልፎ ሰጠው...

Published in ልብ-ወለድ
Monday, 27 May 2013 14:02

አስጨናቂው ጉዞ

ሰማዩ ጨልሟል፡፡ ጨረቃ ወለል ብላ ወጥታ ደማቅ ብርሃኗን ትለግሳለች፡፡ የባህሩ ማዕበል ሲጋጭ የሚፈጥረው ድምጽ ስሜትን ያነቃል፡፡ ከእኔ ጋር ተቀምጠው የሚሄዱትን ተጓዦች በዓይኔ ቃኘሁ፡፡ ሽማግሌ ሸበቶ ቄስ የጣጣፈ ልብሳቸውን ለብሰው እየተጓዙ ልብሳቸውን አሁንም አሁንም ያስተካክላሉ፡፡ አናታቸው ላይ ያደረጉት ቆብ እንኳን ሳይቀር የተጣፈ ነው፡፡ የሚንቀለቀሉት ዓይኖቻቸው ውስጥ ከፍተኛ ብልጠት ይነበባል። ከጐናቸው አንድ ወታደር መለዮውን ለብሶ ተቀምጧል፡፡ ፀጉሩን በፍጥነት እያከከ ዙሪያውን ይገላምጣል፡፡ አንዳች የሚበላው ህዋስ ሳይኖር አይቀርም፡፡ ሌሎችም ብዙ ሰዎች ከእኛ ጋር እየተጓዙ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ካርታ እየተጫወቱ ከመሀል ድንገት ከትከት ብለው ይስቁና ተመልሰው ካርታቸው ላይ ያፈጣሉ፡፡ ማሲንቆውን እየገዘገዘ አንድ አዝማሪ እየዘፈነ ነው፡፡

ሙዚቃውን እንዲያቆም የሚለምኑት ከሚያደምጡት ይበልጣሉ፡፡ ከማሲንቆውና ከድምጹ የትኛው ይበልጥ እንደሚያስጠላ አላወቅሁም። ከሙዚቃው ጋር የማይሄድ በእስክስታና በቫልስ መካከል ባለ ስልት የምትውረገረግ አሮጊት ዙሪያውን እየተሽከረከረች ነው፡፡ ዞሬ ስመለከት የምንሄድበት ነገር ከመርከብ የተለየ እንደሆነ አስተዋልኩ፡፡ ድንጋጤ ሰውነቴን እንደ ጉንዳን ወረረኝ፡፡ የአሣ ቅርጽ ያለው ነገር ነው። አሣ ነው እንዴ? ሊሆን አይችልም፡፡ ከአጠገቤ ያለውን ሰው “የት ነው ያለነው?” ስል ጠየኩት። “ማንም የሚያውቅ የለም” መለሰልኝ፡፡ “እዚህ ስለማይነጋ ቀን መቁጠር አልቻልንም፡፡ የሁላችንም የእጅ ሰአቶች ቀጥ ብለው ቆመዋል፡፡ አንተ ለረጅም ጊዜ ከእንቅልፍህ ስላልነቃህ ብዙዎቻችን ተረብሸን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ስትነቃ ያስተዋለህም የለ!” ፊቱ ላይ የተንኮል ፈገግታ ይታያል፡፡ በሀሳብ ጭልጥ ብዬ ሄድኩ፡፡ የት ነው ያለነው? ወዴት ነው የምንሄደው? እንዴትስ ወደ እዚህ ቦታ ልንመጣ ቻልን? ማለቂያ የለሽ ጥያቄዎች ጭንቅላቴ ውስጥ መንጫጫት ጀመሩ፡፡ በቀስታ ወደ ጥግ ተጠጋሁ፡፡

በእርግጥም ይህ ነገር የአሣ መቅዘፊያዎችና የአሣ ጅራት ያሉት ነው፡፡ አሣ ላይ ሆኖ መጓዝ ግን ቅዠት እንጂ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ መርከባችን ምናልባት የረቀቀ የቴክኖሎጂ ውጤት ሳትሆን አትቀርም፡፡ ግን የሚገርመው ምንም የውስጥ ማረፊያ የሌላት መሆኑ ነው፡፡ ተጓዦች በሙሉ ያለነው ከውጪ ነው፡፡ ድንገት “እንደምን አደራችሁ የተከበራችሁ ተጓዦች” የሚል ድምጽ ከፊት ለፊታችን ተሰማ። ወደፊት ስንመለከት ያናገረን አሣ ኖሯል፤ ትልቅ አሣ፡፡ “ፀሐይ እዚህ ስለማትወጣ ነው እንጂ በምድር ሰአት አቆጣጠር አሁን ነግቷል” የአሣው ድምጽ ውብ ቢሆንም በውስጡ የሚያስፈራ ቅላፄ ያዘለ ነው። ቀድመን መልኩን ያላየነው ራሱን ባህሩ ውስጥ ቀብሮ ስለሚዋኝ እንደነበር ተገነዘብኩ፡፡ ሁላችንም በፀጥታ ተውጠን አሣውን እናዳምጣለን፡፡ “እስካሁን ያላናገርኳችሁ ሁላችሁም እስክትነቁ በጥበቃ ላይ ስለነበርኩ ነው፡፡

ከእናንተ ውስጥ የት እንዳለን የሚነግረኝ አለ?”

አሣው በፊት ከማውቃቸው አሦች የተለየ ነው፡፡ ዐይኑ እንደ ነብር ያበራል፣ ያስፈራል፡፡ “ይህ ህልም እንጂ እውነት ሊሆን አይችልም። ብቻ ለህልም በጣም ረዘመብኝ” አሉና ቄሱ አንገታቸውን አቀረቀሩ፡፡ ግራ ተጋብተዋል፤ ልብሳቸውን አሁን አያስተካክሉም፡፡ አሣው ልቡ እስኪፈርስ በሳቅ ተንፈቀፈቀ፡፡ በጐን የሚታዩኝ ጥርሶቹ በልዘዋል፤ ሰው ቢሆን ሱሰኛ ነው የሚያስብል አይነት፡፡ “አይ መምሬ፤ ህልም ውስጥ ነን ያለነው አሉን! ህልም ቢሆን ምንኛ በታደሉ ነበር፡፡ ሌላ የሚሞክር ይኖራል?” በዝምታ ተዋጥን፤ ዝምታው እየረዘመ ሄደ፡፡ “እሺ እኔው ልንገራችሁ፡፡ ያላችሁት በአንድ የማታውቁት እንግዳ ዐለም ውስጥ ነው፡፡ እዚህ ሁልጊዜ ጨለማ ነው፤ ከጨረቃ በቀር የምትወዷት ፀሐይ አትወጣም፡፡ ከላዬ ላይ ዘላችሁም ወደ ባህሩ ውስጥ መግባት አትችሉም፡፡

ሙታን ናችሁ፣ ሁላችሁም ምድር ላይ ሞታችኋል፡፡” ተጓዦች ይህን ሲሰሙ በድንጋጤ መንጫጫትና ማለቃቀስ ጀመሩ። እኔም ከአጥንቴ ውስጥ ከባድ ቅዝቃዜ ተሰማኝ፡፡ ሞት? ምኑን ኖሬ! ሚስት ልጅ እንኳን ሳይኖረኝ! ወይኔ! አስደንጋጩን ዜና በፀጋ የተቀበለ አልነበረም፤ ሁሉም ከራሱ ስሜት ጋር የሚታገል ይመስላል። ቀድሞ በሀሴት ስትውረገረግ የነበረችው አሮጊት ድንገት እየጮኸች ማልቀስ ጀመረች፡፡ እውነትም ህይወት ለካ አትጠገብም፡፡ አሮጊቷ እንደ ትንሽ ልጅ ሞቷን መቆጨቷ ገረመኝ፡፡ የኔ የአፍላው ነው እንጂ የሚያሣዝነው፤ ከተጓዦቹ በሙሉ በእድሜ ትንሹ እኔ ነኝ፡፡ “ሞታችሁን የማታስታውሱ ምስኪኖች” አለ አሣው በፈገግታ፡፡ “ሰው ከሞተ በኋላ አሟሟቱን እንዳያስታውስ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ መምሬ ግን ለምን ወደዚህ ቦታ የመጡ ይመስልዎታል?” አሣው መጠየቅ በጣም ይወዳል፤ ጥያቄዎቹን ግን መልሳቸውን እያወቀ ነው የሚጠይቀው፡፡ “እኔ ምን አውቃለሁ፤ አንተው ንገረኝ እንጂ” አሉ ቄሱ በተዳከመ ድምጽ፡፡

“ጥሩ ሌላ የሚያውቅ ሰው ይኖራል?” መልሶ ጠየቀ፡፡ “እኔ እንደሚመስለኝ ገሀነብ ውስጥ ነው ያለነው” አለ ወታደሩ መሀል አናቱን እንደለመደው እያከከ፡፡ “አንተ ከጦርነትና ከእሳት ውጭ ምንም የማታወቅ አሳዛኝ ፍጡር ነህ አለው” አሳው በምሬት፡፡ “እዚህ ያላችሁት ለገነትም ይሁን ለሲኦል የማትገቡ ነፍሶች በመሆናችሁ ነው፡፡ ወይ ፀድቃችሁ አልፀደቃችሁ፤ ወይ በሀጢአት ተዘፍቃችሁ አልቦካችሁ! ለሁለቱም ዓለማት የማትገቡ የተኮነናችሁ ነፍሶች!” ይህንን ሲሰሙ ቄሱ አማተቡ። ፍርሃት በመላ ሰውነታቸው ሰርጿል፡፡ “መምሬ” አለ አሳው በፈገግታ “ይህች የሚያማትቧትን ነገር ይተዋት፡፡

በምድር ብዙ የዋሃንን ያታለሉት አይበቃዎትም?” “ማንን ሳታልል አየኸኝ?”

የአምላክን ቃል በቅንነት ከማስተማር ውጭ፣ የእርሱን ታላቅነት ከመመስከር ውጭ ምን ክፉ ተግባር ሳደርግ አየኸኝ?” አሣው ይህን ጊዜ ከመቅጽበት ሲዞር አካባቢው በውሃ መንቦራጨቅ ተረበሸ፡፡ አሣ መዞር እንደሚችል አላውቅም፤ ይሄኛው ግን ይዞራል፡፡ “ታዲያ እኔ ነኝ የሰፈሬን ልጃገረዶች ሳባልግ የነበርኩት?” አስፈሪ ቢጫ አይኖቹን እያጉረጠረጠ አፈጠጠባቸው፡፡ “በእርግጥ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ሰርተዋል፡፡ ስለዚህም ደጉ በክፉ ተጣጥቶ እዚች ቦታ ተገናኘን፡፡” ቄሱ ተናደው “ወጊድልኝ አንተ ክፉ ሰይጣን” እያሉ ለረጅም ጊዜ ጮሁ፡፡ የአሣው ትዕግስት እንዳለቀ ፊቱ ላይ ይነበባል፡፡ ድንገት በብርሃን ፍጥነት ቄሱን ጐረሳቸውና ያላምጣቸው ጀመር፡፡ ብዙ ካላመጠ በኋላ ዋጣቸውና ቆባቸውን ወደ ባህር ተፋ፡፡ ይህን ያዩ ተጓዦች በሽብርና በድንጋጤ ተዋጡ፡፡ ብዙዎች እየተንደረደሩ ወደ ባህሩ ለመዝለል ቢሞክሩም ወደ አሣው ጫፍ ሲደርሱ እግራቸው እያጥለመለመለ ጣላቸው፡፡ “አይ መምሬ ለሚወዱትም ገነት ይሁን ለሚፈሩት ሲኦል ሳይበቁ ሆዴ ውስጥ ቀሩ፤ ከመኖርም ወደ ምንምነት ተሸጋገሩ” አለ አሣው በፀፀት፡፡

ድንገት እምባው ዱብ ዱብ እያለ መውረድ ጀመረ፡፡ “እኔም ተርቤ ነው እንጂ እሳቸውን መብላት አልነበረብኝም ነበር፡፡ አያችሁ እዚህ ባሕር ውስጥ የሚበላ አንዳችም ፍጡር የለም፤ ቢሆንም በድርጊቴ በጣም ተፀጽቻለሁ፡፡ ሁላችሁንም ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ” አለና አሣው በሚያሳዝን ድምጽ እንደ ውሻ ማላዘን ያዘ፡፡ እኔም የአሣውን መረበሽና ከልብ ማዘን ሳይ ልቤ በሀዘን ተነካ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አሣው ሀዘን እንደሚበቃንና የተከፋ መንፈሳችንን ማስደሰት እንደሚኖርብን ተናግሮ፣ አዝማሪውን ጥሩ ሙዚቃ እንዲያንቆረቁርልን ነገረው፡፡ አዝማሪውም ድምፁን ከጠራረገ በኋላ ማሲንቆውን እየገዘገዘ ማንጐራጐር ጀመረ፤ ለጆሮ በፍፁም የማይጥም ሙዚቃ፡፡ አሳው ግን ልቡ ተነክቶ፤ አይኑን ጨፍኖ በተመስጦ ይሰማ ጀመር፡፡ አብዛኛው ሰው ሙዚቃውን አልወደደውም፡፡ ተወዛዋዧ አሮጊት እንኳን በዚህ ጊዜ አትወዛወዝም፡፡ ፊቷን አኮሳትራ ሁኔታውን በመከታተል ላይ ነች፡፡ አዝማሪው ሙዚቃውን ቀጠለ፤ ቀጥሎም በግጥሙ አሳውን አሞካሸ፡፡ አሳው ፍርድ አዋቂና የሰው ልክ አዋቂ፣ ጥሩ ከሳሽና ጥሩ ዳኛ እንደሆነ ያለማቋረጥ ለፈፈ፡፡

አሳው በተመስጦ ሙዚቃውን ያዳምጣል፣ ራሱን አልፎ አልፎ ይነቀንቃል፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ አዝማሪው ሙዚቃውን ጨረሰ፡፡ ፊቱ ላይ ላቡ ችፍ ብሏል፡፡ አሳውን ለማስደሰት ብዙ ታግሏል፣ ብዙ ደክሟል። “አዝማሪ ሙዚቃ አለቀ እንዴ?” ሲል አሳው ጠየቀው፡፡ አዝማሪውም በአዎንታ ራሱን ነቀነቀ፡፡ አሳው በዚህን ጊዜ ከመቅጽበት ዞረና አዝማሪውን ጐርሶ አይኑን እኛ ላይ እያጉረጠረጠ ማላመጥ ጀመረ፡፡ አዝማሪውንም ውጦ ማሲንቆውን ወደ ባህሩ ተፋው፡፡ አሮጊቷ በድንጋጤ ኡኡታውን አቀለጠችውና ተዝለፍልፋ ልትወድቅ ስትል ካጠገቧ ያሉ ሰዎች ደገፏት፡፡ ከወንዶችም ብዙ ያለቀሱ አሉ፡፡ “ድንቅ አዝማሪ ነበር፤ ሆዴ ውስጥ ሆኖ እንዲያንጐራጉር ስለፈለግሁ እንጂ እሱንስ መብላት አልነበረብኝም” አለና አሳው ምርር ብሎ አለቀሰ፡፡ እንባው በዚህ ጊዜ የአዞ እንባ ሆነብኝ፡፡ ውስጤም በጣም ጠላው፡፡ “ዛሬ በስራዬ ስለተፀፀትኩ ከእናንተ ጋር እንደ ልቤ መጫወት አልችልም፡፡ እናንተው ተጫወቱ” ብሎ ጭንቅላቱን ወደ ባህር ውስጥ ከተተ፡፡ በአሳው ተግባር ሁላችንም በጣም ተረብሸናል፣ አዝነናል፣ ተናደናል፡፡

እኔም ይሄንን አጋጣሚ ተጠቅሜ መመካከር እንዳለብን እየዞርኩ ተናገርኩና ተሰበሰብን፡፡ ወታደሩ በቁጣ እራሱን እያከከ አሳው እንደዚህ የሚቀጥልበት መንገድ መኖር እንደሌለበት ተናገረ፡፡ ወደራሱ ስመለከት መሀል አናቱ ላይ ቀዳዳ ተመለከትኩ፡፡ የሚያሳክከው ጥይት በመሀል አናቱ የገባበት ቦታ ላይ ነው፡፡ የሞቱ መንስኤ ጥይቱ ሊሆን እንደሚችል ጠረጠርኩ፡፡ “ስንት ምሽግ የሰበርኩ፣ ጠላቴን ያንበረከኩ ጀግና ነኝ፡፡ ዝም ብዬ የአሳ እራት እስክሆን የምጠብቅበት ምክንያት አይታየኝም። ”“ምን መፍትሔ አለህ?” አንድ ፊቱ የሚያሳዝን ሰው ከመካከላችን አቋረጠው፡፡ “ጥሩ ጥያቄ ነው” አለ ወታደሩ ወኔ በተሞላ መንፈስ፡፡ “ጠላትን ለማሸነፍ የሚያስፈልገው ዋናው ነገር ትብብር ነው፡፡ ጠላት ይመጣብኛል ብሎ በማያስብበት ቦታና ወቅት ማጥቃትና አከርካሪውን መስበር ድልን ያጐናጽፋል።” ቀጥሎም በህይወት ሳለ እንዴት የጠላት ምሽግ እንደሰበረና የጀብድ ተግባር እንደፈፀመ ያለማቋረጥ ተናገረ፡፡ “ይህ ሁላ ከአሳው ጋር በምን ይገናኛል?” ስል ጠየቅሁት ትዕግስቴ ተሟጦ፡፡ “ምን ማለትህ ነው? በደንብ ይገናኛል እንጂ እኔ እኮ የምላችሁ ድንገት አሳው እራሱን እንዳሁኑ ባህር ውስጥ እንደቀበረ ብናጠቃው ከመጥፋት እንተርፋለን” ነው፡፡

ግማሾቻችን ጅራቱን፣ ግማሻችን መቅዘፊያውን ሌሎቻችን ራሱን ይዘን ብንቀጠቅጠው መቼም መሞቱ አይቀርም” አለ በጥርጣሬ፡፡ ወኔው ፊቱ ላይ ያበራል፤ ዐይኖቹ ላይ እልህ ይንቀለቀላል። ይህን ወደል አሳ መግደል ወታደር ቤት አይማሩት ስለዚህ አይፈረድበትም፣ ካቅሙ በላይ ቢሆን ነው እንጂ፡፡ ብዙዎቻችን ከአሳው ጋር ግብግብ መፍጠር የሚደፈር ተግባር ሆኖ አላገኘነውም፡፡ እንደ አንድ አማራጭ ግን ልንይዘው ተስማማን፡፡ ሌላ ሃሳብ ያለው ሰው እንዳለ ጠየቅሁ፡፡ አንድ መነጽር ያደረገ ሰውዬ ሃሳብ እንዳለው ተናገረ፡፡ ብዙ የተማረ ይመስላል፡፡ ፀጉሩ ሽበት ጣል ጣል ያለበት ነው፡፡ “እኔ በሙያዬ ሳይካትሪስት ነኝ እናም እዚህ አሳ ላይ ያየሁት ችግር ለኔ አዲስ ያልሆነና ብዙ ታካሚዎቼ ላይ ቀድሞ ያየሁት ነው፡፡ ፈረንጆች ደብል ወይም መልቲፕል ፐርሰናሊቲ ዲስኦርደር ይሉታል፡፡ ሁለትና ከዛ በላይ የሆኑ ተቃራኒ ባህርዮች አንድ ሰው ላይ የሚታዩበት ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ ይህ ችግር ያለበት ሰው በአንድ ወቅት ተቆጪና አስቸጋሪ ሲሆን ሌላ ወቅት ላይ ደግሞ ለሰው ተስማሚና ፍፁም ደስተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ እናም ሁለቱ ባህሪዎች አንዱን ሰው እንደ ሁለት የተለያዩ ሰዎች ያደርጉታል፡፡ አሳው እንዳያችሁት ቄሱንና አዝማሪውን እንደበላ በፀፀት ሲያለቅስ ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው የማንነት ግጭት በውስጡ እንደተቀበረ ነው፡፡ በልጅነቱ ሳይኮሎጂካሊ አብዩዝድ የሆነ አሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ከኔ ጋር አንድ ሴሽን ቢኖረን ያለውን ችግር በደንብ ልረዳና አብረን መፍትሄ የምንፈልግበት ጥሩ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል” ሲል ጨረሰ፡፡

ሀሳቡን ብዙዎች ተቀበሉት፡፡ አሳው ለግዳዮቹ ማልቀሱ ከተለመደው ባህርይ ውጭ ነው ሲሉ መሰከሩና ይህን የሳይካትሪስቱን ሀሳብ እንደ አንድ አማራጭ እንድንይዘው ተወሰነ፡፡ ወዲያው አንድ ቅልብልብ ወጣት “እኔ ሌላ ሀሳብ አለኝ” አለ፡፡ ሲናገር በጣም ይፈጥናል፤ መላ ሰውቱ ይወራጫል፡፡ “በህይወት ሳለሁ ጠበቃ ነበርኩ። እናም ብዙ የህግ ክሶችን ረትቻለሁ፡፡ አሳው ከእንግዲህ አንድ ሰው ቢበላ በህግ ተጠያቂ ከመሆን እንደማያመልጥ ልንነግረው ይገባል፡፡ የሰው ልጅ በሰውነቱ ክቡር ነው እናም በነፃነት የመኖር መብቱን ማንም ጉልበተኛ ነኝ የሚል ሀይል በኢሰብአዊ ሁኔታ ሲገፍፈው የመቃወም መብት እንዲሁም ግዴታ አለበት፡፡” ልጁ ንግግሩን ሳይጨርስ ተወዛዋዧ አሮጊት “እኛ እኮ ሞተናል፣ አንተ የምትለው ህግ ለህያዋን እንጂ ለእኛ አይሰራም፡፡ የሙታንን መብት የሚያስከብር አንዳችም የሕግ አካል የለም” አለች ወገቧን በእጆቿ ጥርቅም አድርጋ ይዛ፡፡ ወጣቱ ጠበቃ መናገሩን ቀጠለ፡፡ “መርሳት የሌለብን አንድ እውነታ አለ፡፡ እኛ እኮ ምድር ላይ ብንሞትም እዚህ አሁን ያለንበት አለም ላይ ህያዋን ነን፡፡ እየኖርን እስከሆንን ድረስ ደግሞ በምድር የምናውቀው አይነት ሕግ ሊኖረን ይገባል፡፡ አለበለዚያ አንዳንዶቻችን ሌላዎቻችንን እየጨፈለቅን ኢፍትሀዊ የሆነ አኗኗርን እንደ ትክክለኛ የኑሮ ስርዓት ልንቀበል ነው፡፡

ይህን ሆዳም አሳ ከእንግዲህ በሕግ ከሰን መጠየቅ ይኖርብናል! ነገሮች በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይችሉም!” የጠበቃው ሀሳብ ለብዙዎቻችን ባይዋጥልንም ልጁን ላለማስቀየም ያቀረበውን ሀሳብ እንደሌላ አማራጭ አድርገን እንድንወስደው ተናገርኩና ሁላችንም ተስማማን፡፡ ቀጥሎም አንድ ኩሩ ወፍራም ቦርጫም ሰውዬ መናገር ጀመረ፡፡ “በህይወት ዘመኔ በፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውቻለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ከመሆን ባሻገር የከተማ ከንቲባ ሆኜ ለረጅም አመታት አገሬን አገልግያለሁ፡፡ እና አንድ የታዘብኩት ነገር ቢኖር እናንተ ያለንበትን ችግር አሳሳቢነት ጠልቃችሁ አለመረዳታችሁን ነው፡፡ መሪ የሌለው ስብስብ ችግር ሲኖር ወዲያው ይፈረካከሳል፡፡ እናም በቅድሚያ የስልጣን ተዋረድ ሊኖረን ይገባል!” ከጎኑ ያሉ የተወሰኑ ሰዎች ታላቅ ንግግር የሰሙ ይመስል አጨበጨቡ። ሰዎቹ በህይወት ሳሉ ከከንቲባው በታች የነበሩ ባለስልጣኖችና ተከታዮቻቸው እንደነበሩ ተረዳሁ፡፡

በህይወት ሳሉ ሰውዬውን መከተል አባዜ ሆኖባቸው እዚህም ተከታዮች መሆናቸውን አላቋረጡም፡፡ ከንቲባው በእርካታ ንግግሩን ቀጠለ፡፡ “ስለዚህም በቅድሚያ ፍትሀዊ የመሪ ምርጫ መካሄድ አለበት። እኔን መሪያችሁ አድርጋችሁ ከመረጣችሁ ችግሩን በአፋጣኝ የምፈታበትን መንገድ አሳያችኋለሁ፡፡” ወታደሩ ድንገት አቋርጦ “ለምርጫና ለማያስፈልግ ቢሮክራሲ አሁን ጊዜ የለንም፡፡ ይልቁንስ መፍትሔ ካለህ ብትነግረን ይሻላል” አለው፡፡ ወታደሩ ስሜቴን ስለተናገረልኝ ደስ አለኝ፡፡ “አሁንም እያዳመጣችሁ አይደለም፡፡ ያለ ስርአታዊ አወቃቀር ማንኛውንም ስራ መስራት ለውድቀት የሚዳርግ ነው፡፡ እኔን ከመረጣችሁኝ አሳውን ከውጭ ሆነን ልናጠምደው እንደማይሳነን የምታዩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡” ይህ ፖለቲከኛ ባዶ ተስፋዎችን ለስልጣን ጥማቱ ሲል ሊሸጥልን እንደሚሞክር ተሰማኝ፡፡ ስልጣኑን ቢያገኝ አሁን ምን ይጠቅመዋል? ግን ማን ያውቃል፤ ከአሳው ጋር ተመሳጥሮ ቢያስፈጀንስ?

አብዛኛዎቻችን በጭንቀት ስሜት ውስጥ ሆነነ የስልጣን ርብርቦሽ ለማየት ፈፅሞ ስላልፈለግን ሀሳቡን አጣጣልነው፡፡ ደጋፊዎቹም ሆኑ ከንቲባው የሚያዳምጣቸው ሰው አጡ፡፡ “እኔ በተነሱት ሀሳቦች አልስማማም” አንድ ራሰ በራ ሰውዬ ነበር፡፡ “በሙያዬ የባዮሎጂ መምህር ነበርኩ፡፡ ተፈጥሮ የራሷ ህግ አላት፡፡ ጠንካራው ደካማውን እየደቆሰ መኖሩ ግድ ነው፡፡ አንበሳ ለመኖር ሲል ሚዳቋን ቢበላት አይገርምም፡፡ ቻርልስ ዳርዊን ሰርቫይቫል ኦፍ ዘ ፊተስት ያለውም ይሄንኑ ነው፡፡ ይህ አሳ ምንም ነገር በሌለበት ባህር ውስጥ የሚመገበው ነገር ስለሌለ እኛን ቢበላን ጥፋቱ ምን ላይ ነው?” ከፖለቲከኛውም የባሰ በመምጣቱ ተገረምኩ፡፡ ይህ የሁላችንንም ጥፋት በፀጋ የሚቀበል ጎጂ ሀሳብ በሁላችንም ዘንድ ተቀባይነት አጣ፡፡ እስካሁን የተነሱትን ሀሳቦች በተቀባይነታቸው ቅደም ተከተል እንዲሞከሩ ተነጋገርንና በቅድሚያ የሳኪያትሪስቱ ካልሰራ የህግ ባለሙያው፣ ያም ካልሆነ የወታደሩ ሀሳብ እንዲሞከር ወስነን ተበታተንን፡፡ እኔም ጥጌን ይዤ ማውጣት ማውረድ ጀመርኩ፡፡ ከሀሳባችን አንደኛው ይሳካ ይሆን? ወይስ የአሳው መብል ከመሆን አንድንም? መልሱን ጊዜ ነው የሚያውቀው፡፡ በዝግታ ባህሩን እየቃኘሁ በሀሳብ ነጎድኩ፡፡

Published in ልብ-ወለድ

ተከታዮቹ ሁለት ሥነ ጽሑፋዊ እሳቤዎች ፤ ደጋፊ እና ነቃፊ አግኝተው በመላው ዓለም የሚገኙ ጸሐፍትን ፤ ሀያሲያንን እና አንባቢያንን ሲያሟግቱ ኖረዋል፡፡ ሙግቱ አሁንም የተቋጨ አይመስልም፡፡ ወደፊትም መቋጨቱን እንጃ፡፡ የመጀመሪያው እሳቤ በደምሳሳው ‹‹እውነት ልቦለድ ስትሆን የሥነ ጽሑፍ ሞት ተቃርቧል›› የሚል ነው። ይህ እሳቤ በዚያው በሥነ ጽሑፉ ክበብ በርካታ ደጋፊዎችና አቀንቃኞች አሉት፡፡ ሁለተኛው እና ተቃራኒው እሳቤ ‹‹ በሥነ ጽሑፍ እውነትን እንዳለች ማቅረብ ፎቶ ከማንሳት ምንም አይለይም›› የሚል ነው፡፡ ይኸኛው ሀሳብም እንዲሁ በርካታ ደጋፊዎች አሉት፡፡ የዚህ ሀሳብ አቀንቃኞች እውነትን ኪናዊ ለዛን ፤ ውበትንና ጣእምን ተላብሳ ሲያነቧት ነው ሀሴት የሚያደርጉት፤እውነትን በደራሲው ውብ ቃላት፤ በሳል ዕይታ ፤ማራኪ የህይወት ትዝብትና ምትሀታዊ ትረካ ስጋ ለብሳ ፤ነፍስ ዘርታና ሙሉ ህልውናዋን ተጎናጽፋ ማግኘት ነው የሚፈልጉት።

ዛሬ ለዳሰሳ የመረጥኩት ‹‹የመንጌ ውሽሚት›› የልቦለድ መጽሐፍ በነዚህ ሁለት ምድቦች አማካይ መንገድ ላይ የሚዋልል ይመስላል፡፡ ዐቢይ ጭብጡን አብዝተን በምንወደው የልጅነት ሕይወት ላይ ያደረገውን ይህን ማለፊያ የረጅም ልቦለድ የመጀመሪያ ሥራውን ጀባ ያለን ተስፋዬ አለነ አባተ ነው፡፡ ልክ በልጅነት ዘመን እንዳነበብነው በማክሲም ጎርኪ ‹‹ ልጅነት ›› ውስጥ እንዳሉት ገጸ ባህሪያት ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በዘነበ ወላ ‹‹ ልጅነት›› ልቦለድ ውስጥ በእጅጉ በሳቅ እንዳፍነከነኩን እነ ቀጢሳው፤ በአዳም ረታ ተወዳጅ የረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› ውስጥ ንፋስ መውጫ ጉብታ ላይ ሆኖ ሕይወትንና ዓለምን በሕፃን አዕምሮው እንደሚታዘበው መዝገቡ ዱባለ እንዲሁም ‹‹ እንጀራዬን››፤ ‹‹ ዘላን››፤ ‹‹ ጢቦ›› እና ‹‹ከሰማያዊ ወደ ቦቢ›› በተሰኙት የአዳም ረታ አጫጭር ልቦለዶች ውስጥ እንደሚገኙት ሕፃናት፤ በእንዳለጌታ ከበደ የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ‹‹ከጥቁር ሰማይ ስር›› ውስጥ እንደሚገኘው አዝናኝ ሕፃን አቦቸር ሁሉ በ‹‹ በመንጌ ውሽሚት›› ውስጥ የሚገኙት አበይት ሕፃናት ገፀ ባሕሪያት ‹‹ጭንቅሎ››፤ ‹‹ጠይሜ›› እና ‹‹ጠምቤ››ም በመጽሐፉ ደራሲ መቼም ከአእምሮ እንዳይወጡ ሆነው ተቀርጸዋል ፡፡

ደራሲው ተስፋዬ አለነ ‹‹መንደርደሪያ›› በሚል ርእስ ባቀረበው መግቢያ ላይ ‹‹የመንጌ ውሽሚት የኔና የጓደኞቼ የነጭንቅሎ ፤ ጠይሜ ፤ጠምበለልና የመሳሰሉት ሕይወት ብቻ አይደለም - የናንተም ያኔ ልጅ የነበራችሁ ሰዎች ሁሉ ጭምር እንጂ …›› ይላል ፡፡ ያንን ሲለን እንዲያው ‹‹ለራስ ሲቆርሱ…›› ብለን ደራሲው ራሱን እየሸጠ ነው ብለን በትዝብት ገርፈነው እናልፈዋለን፤ኾኖም ታሪኮቹ የእውነትም እንደሚመለከቱን የምናውቀው ጥቂት ገጾችን እንደገለጥን ነው፡፡ በእርግጥም በመጽሐፉ ውስጥ ካሉት ታሪኮችና ገጸ ባህሪያት ውስጥ የልጅነት ሕይወታችንን የወከለልንን ሕጻን ፈልገን ማጣት አይቻለንም፤ የሕይወት ትወናችንን እንመለከትበታለን፡፡ በገዛ ልጅነታችን እንስቃለን፣ ፎቶ ባልነበረበት ዘመን የተወለድን ጭምር እንስቃለን፣ እድሜ ለዚሁ ደራሲ ራሳችንን በፊደል ቀርጾ በመጽሐፍ ገጾች አትሞ፣ የልጅነት ፎቶዎቻችንን ያድለናልና፡፡ እስኪ መጸሐፉን በወፍ በረር እንቃኘው፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ለዚህ ዳሰሳችን በማጣቀሻነት የተጠቀምኩት የመጽሐፉን ሁለተኛ እትም እንደሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ከሚገኙት ሀያ አንድ ታሪኮች ውስጥ ለመጽሐፉ ርእስነት የተመረጠው ‹‹የመንጌ ውሽሚት›› የሚለው ታሪክ ፤በመጽሐፉ የመጀመሪያ ምእራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ጭንቅሎ የተባለው ገጸ ባህሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኀይለማርያም በወጣትነት ዘመኑ ሐረር፤ ቀላድ አምባ ውስጥ በጥገና ሥራ ተሰማርቶ ሳለ፣ አጎቱና የሰፈር ሰዎች የነገሩትን ይዞ፤ በመንጌ የከንፈር ወዳጅነት የሚታሙትን እማማ ትሁኔን ስለሰማው ሀሜት ይጠይቃቸዋል፡፡ እማማ ትሁኔ አረቄ ሻጭ ናቸው፡፡ በእማማ ትሁኔ አረቄ ቤት ግድግዳ ላይ ‹‹ዱቤ ከመንግሥቱ ወዲህ….›› የሚለውን የጽሑፍ ማስገንዘቢያ ወንድሙ አረቄ እንዲገዛ ሲልከው የተመለከተው ጭንቅሎ፣ እግረ መንገዱን የማስገንዘቢያውን ምንነት ለማወቅ እማማ ትሁኔን ይጠይቃል፡፡ ጭንቅሎ በሕጻን አንደበቱና አእምሮው በሀሜት መልክ የሰማውን ወሬ እውነትነት ለማጣራት የሚያደርገው ጥረትና ትህትናው አስደማሚ ነው፡፡

እማማ ትሁኔም እንዲህ ሲሉ ይመልሱታል፡- ‹‹…መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ያኔ ገና ወታደር ሳለ እዚህ ጥገና የሚባለው የወታደር መሥሪያ ቤት ውስጥ ነበር የሚሠራው፡፡ እንዴት ያለ ጎበዝ መካኒክ ነበር መሰለህ …ታዲያ አንድ ጊዜ ደምወዝ እስኪወጣ በዱቤ ጠጣልህ፡፡ ከዚያ ከዛሬ ነገ ይከፍለኛል ስል ሲቀር፤ ስጠብቅ ሲቀር ኋላ ላይ እኝያን ደግ አባት ከመንበረ ስልጣናቸው ገልብጦ ገድሏቸው ነገሰ። ግሪሱን ጠራርጎ ዙፋን ላይ ተቀመጠ፡፡ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድራት እሱ ነው›› የሚል ወሬ ሰማሁ። ያን ቅንነቱ አውቅ ስለነበር መንጌ መቼም ጨክኖ ብሬን በልቶ አይቀርም። እጥፍ አድርጎ ይመልስልኛል ብዬ በተስፋ ጠበቅኩት፡፡ ለአንድ ሀገር አስተዳዳሪ አረቄ በብድር ያጠጣሁ መሆኔን በኩራት ለሀረር ሕዝብ እያወራሁ ከረምኩ፡፡ በመጨረሻ ምላሴ ሌላ እዳ ይዛብኝ መጣች ›› መንጌን የተመለከቱት ትርክቶች ታሪክ ቀመስ በመሆናቸው ልቦለድ ይሁኑ ፈጠራ እንዲሁ እንደተወዛገብን ታሪኩ ይፈጸማል፡፡ ደራሲው የሀረር ልጅ መሆኑና ለልቦለድ የራቁ፣ ለእውነታ የቀረቡ ታሪኮችን ይዞልን ስለቀረበ፣ ‹‹የመንጌ ውሽሚትን›› ታሪክ እውነት ይሁን ስነጽሁፋዊ ኩሸት የምናውቀው ነገር አይኖረንም፤ ደራሲውም ውዝግባችንን የፈቀደ ይመስል ምንም ፍንጭ አይሰጠንም፡፡

ለቤተሰባቸው እና ለእናት አገራቸው ሟች ናቸው ብለን የምንዘክራቸው ቆራጡ መንጌ የጉርምስና ህይወት ደራሲው እንደነገረን አይነት ላይሆን እንደሚችል ልባችን መጠርጠሩ አይቀርም፡፡ ‹መንጌ ዉባንቺን ከማግኘታቸው በፊት በእርግጥም የጭን ገረድ ነበራቸውን?› ብለንም እንጠይቃለን፡፡ ደራሲው ይህንን ክፍል በታሪክ ላይ ተመስርቶ መጻፉ ነው ለዚህ ሁሉ የሚዳርገን፡፡ በሌላ ታሪክ ውስጥ ጭንቅሎ በህጻንነታችን የቃለ መሀላን ክብደት ሳንገነዘብ የተናገርነው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ የምንፈጽማቸውን አስገራሚ መሀላዎች ያስታውሰናል፡፡ የመሀላ ታሪኮቹን ደራሲው የጻፈበት ክፍል ፈገግታን ማጫሩ የግድ ነው፡፡ በእናቶቻችን ስም እንፈጽም የነበረውን የመሀላ ብዛት ያስታውሰናል፡፡ በታሪኩ ውስጥ ጭንቅሎና ጠምቤ በእድሜ በጥቂቱ የሚተልቃቸው ጠይሜ በብይ ጨዋታ በቁማር የሚያገኘውን ሳንቲሞች አባቱ እንዳያገኙበት ቆፍሮ ከሚደብቅበት የገዛ ግቢያቸው ውስጥ አውጥተው ይወስዱበታል ::

ጠይሜ ጓደኞቹ ሳንቲሞቹን አለመውሰዳቸውን የሚያረጋግጠው እንዲምሉለት በማድረግ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ ጭንቅሎ እንዲህ ሲል ይተርከዋል:: ‹‹የልጅነት አበባዬን ይቅጨው!›› እያልኩ በውሸት ብዙ ጊዜ ምያለሁ፡፡ አንዴም ግን ተቆጥሮብኝ አያውቅም፡፡ እናቴ ሳትሞትብኝ ቤት እያለች ‹የእናቴ አጥንት እሾክ ሆኖ ይውጋኝ!› ብዬም አውቃለሁ። እናቴ ግን እስካሁን በህይወት አለችልኝ፡፡ ረጅም እድሜ ለሷ! ረጅም እድሜና ጤና ለእናቴ! አምላክ በልጅነታችን የመሀላን ክብደት እንደማንረዳ ስላወቀ መሰለኝ ይቅር ያለኝ ፤ይቅር ያለን ፡፡ ‹‹የመንጌ ውሽሚት›› ዐቢይ መቼት ሀረር ነው። ደራሲው ተስፋዬ አለነ በጭንቅሎ፤ በጠይሜና በጠንቤ በኩል በውብ ቋንቋ የሚተረክልን የሀረርን የልጅነት ህይወት ነው፡፡ እነዚያን ሁሉ የልጅነት ታሪኮች ከደቂቃ በፊት የተከሰቱ ያህል ፤ደራሲው የልጅነት ዘዬአችንን አንድም ሳይቀር ማስታወሱ በእጅጉ አስደምሞኛል፡፡ ቦታ፤ አገርና ርቀት ሳይወስናቸው የልጅነት መልኮቻችን ተመሳሳይ እንደሆኑ ይህ መጽሐፍ አጠናክሮልኛል፡፡

ማክሲም ጎርኪ የተረከው የራሺያ ልጅነት፤ ዘነበ ወላ በ‹ልጅነት› የተረከው የጨርቆስ (አዲስ አበባ ) ልጅነት ፤ አዳም ረታ በ‹ ግራጫ ቃጭሎች ›ውስጥ ያቀረበልን የንፋስ መውጫ ( ጎንደር) ልጅነት፣ ተስፋዬ አለነ ‹‹በመንጌ ውሽሚት› ካቀረበልን የሐረር የልጅነት ሕይወት ጋር የሚያስተሳስራቸው አንድ ክር ያለ ይመስላል፤ በሁሉም ውስጥ አብዝተን የምንናፍቀውን የህፃንነት ዘመን የሕይወት ትወናችንን እናገኛለን። በሕፃን አእምዕሯችን እውነት ላይ ለመድረስ፤ ሕይወትን ለመረዳት፤የአዳዲስና እንግዳ ነገሮችን ምንነት ለማወቅና ለመገንዘብ የምናደርገው የሐሳብ አርምሞና ተመስጦ በሁሉም ውስጥ ይስተዋላል፡፡ ‹ለከፋ› በሚለው ታሪክ ውስጥ ጭንቅሎ አዲስና እንግዳ የሆነበትን ነገር ለመረዳት የሚያደርገውን ጥረት እንመልከት፡- ‹‹…ይሄ .. ክብረ ንጽህና የሚባለው ነገር ምን ዓይነት እቃ ቢሆን ነው በጉልበቱ የወሰደባት? ግራ ገባኝ፡፡ ‹‹ቀለበት፤ ሀብል፤ ኮፍያ፤ ፎጣ፤ ደብተር ተነጠቁ !›› እንጂ ‹ክብረ ንጽህና ተነጠቁ›› ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ እናቴን እሷም ክብረ ንጽህና እንዳላትና እንደሌላት፤ እንደተነጠቀችና እንዳልተነጠቀች ወሬያቸውን ሲጨርሱ እንደምጠይቃት ተማምኜ ማድመጤን ቀጠልኩ።… ‹‹ለከፋ›› እና ‹‹ከእብደት በስተጀርባ›› በሚሉት ታሪኮች ውስጥ ተስፋዬ አለነ የእብደትን ልዩ መልኮች ያስቃኘናል፡፡ ብሪቱ፤ ዘርፌ (ዘርፈሽዋል)፤ ቀሽቲ፤ ተወልደ እና መሊ ( ሚሊዮን) አስገራሚ የአዕምሮ ሕሙማን ናቸው፡፡ ከእብደቷ በስተጀርባ ቀሽቲ ልዩ ተልዕኮ አላት፤ በአለባበስና በድምጽ ፆታዋን ቀይራ፤ ራሷን ጥላ፤ ድሪቶ ለብሳ፤ ትራፊ በልታ በኦሮምኛ እየቀባጠረች ለኦነግ ትሰልላለች፡፡

ጭንቅሎ፣ ጠይሜና ጠምቤ በድንጋጤ አፋቸውን እስኪይዙ ድረስ የቀሽቲን መጨረሻ በዐይናቸው ይታዘባሉ፡፡ በመጽሐፉ ‹‹የፈረንሳይ ካራቴ›› በሚለው ታሪክ ውስጥ ጭንቅሎ ለየት ያለ የቪዲዮ ቤት ገጠመኙን ይተርክልናል፤ ትንፋሻችንን ቁ-ር-ጥ-ቁ-ር-ጥ እስኪልብን ድረስ፡፡ ታሪክን በጽሑፍ በመተረክ እንደሲኒማ የሰውን ትኩረት ይዞ መቆየት መቻል ብዙ ደራሲዎች የሚታደሉት ስጦታ አይደለም፡፡ … ማሙሸት ቪዲዮ ቤት፣ የተመረጡ ጎረምሶች ብቻ ሲመሻሽ አንድ ፊልም በሽልንግ ያያሉ፡፡ማንኛውም ሙጫጭሬ መክፈል ቢችልም መግባት አይፈቀድለትም፡፡ የፊልሙ ማስታወቂያ ብዙ ጌዜ እደጅ አይለጠፍም፡፡ ፊልሙ ሚስጥር ነው፡፡ እኔና ጠንቤ አናውቅም፡፡ ጠይሜ ግን የሆነ ጭምጭምታ ሳይሰማ አልቀረም፡፡ ወንድሙ የማታ ማታውን ፊልም ማየት ስለሚፈቀድለት አውርቶለት ይሆናል፡፡.. ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ‹‹ የቢሾፍቱ ቆሪጦች›› በተሰኘው ልቦለድ ውስጥ የቢሾፍቱ ሕፃናትን ‹‹ማቲዎች›› እያለ ይጠራቸዋል፡፡ ተስፋዬ አለነ ከላይ ከመጽሐፉ በቀነጨብነው አንቀፅ እንደተመለከትነው የሐረር ሕፃናትን ‹‹ሙጫጭሬ›› ይላቸዋል። የአዲስ አበባ ደራሲያን በበኩላቸው ህፃናትን በድርሰቶቻቸው ውስጥ ‹‹ፈልፈላዎች›› ሲሏቸው እንመለከታለን፡፡

ሕጻናት በቢሾፍቱ፣ በሐረርና በአዲስ አበባ እንዲህ በተለያየ ቃል ይገለፃሉ፡፡ አማርኛው በዚህ መልኩ ከሁሉም ቃላትን እየወሰደ ይዳብራል፡፡ ጭንቅሎ አስገራሚ የቪዲዮ ቤት ገጠመኙን መተረኩን ቀጥሏል፡፡ … …ለመጀመሪያ ጊዜ ፈረንሳይ ካራቴን ያየሁት ከእህቴ ከመሳይ ጋር ነበር፡፡ ታገል፤ መሳይን ይዣት ከመጣሁ ሁሌ ፊልም በነጻ እንደሚያስገባኝ ቃል ገባልኝ፡፡ ብቻዬን …እነ ጠይሜን ትቼ መግባት እንደማልፈልግ ነገርኩት፡፡ ለሦስታችንም በነጻ ፈቀደልን፡፡ መሳይን አስይዤ ጓደኞቼን ፊልም ጋበዝኩ፡፡… የመጽሐፉ ደራሲ ተስፋዬ አለነ፤ በዚህ የመጀመሪያ የልቦለድ ድርሰቱ የሐረርን የልጅነት ዘመን በጥልቀትና በስፋት ማስቃኘቱ እንዳለ ሆኖ፤ እግረ መንገዱን ከሁለት ዓሥርት ዓመታት በፊት በሐረርና በዙሪያዋ የነበሩትን ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኹነቶችን ኪናዊ በሆነ መልኩ አቅርቦልናል፤ ከኪነ ጥበብ ሥራ በላይ ዘመንን ቁልጭና ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳይ የለምና ተስፋዬም በ ‹‹መንጌ ውሽሚት” በወቅቱ የነበረውን ሁለንተናዊ የዘመን መንፈስ በደንብ ያሳያል- የዘመኑ አስከፊ ገጽታም አይቀረውም፡፡ ለአስረጂነት በመጽሐፉ ገፅ 191 ላይ የሚገኘውን ተከታዩን ክፍል መመልከቱ በቂ ነው፡፡ …የደንገጎው ውጊያ በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ‹በኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ›ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው ወጣቶች አንዱ የሆነው ፊልጶስ ሰለሞንን የበላ የጦር አውድ ሆኖ አልፋል፡፡ እኚያን ኳስ ለመምታትም ለመሮጥም ፈጣን የነበሩ እግሮች ከባድ መሳሪያ ጎመዳቸው።

ፊሊጶስ በቅጽበት ያፈረሱትን መልሰው መገንባት በማይችሉ ሰዎች በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ተመትቶ ግማሽ ሰው ሆነ፡፡ ከወገብ በላይ እንጂ ከወገብ በታች አካል የሌለው አዲስ ፍጥረት። ከመሰቃየት እንዲገላገል አብረውት በውጊያው ተሰልፈው የነበሩት አባቱ ሻምበል ባሻ ሰለሞን ገብረ እየሱሰ፤ዓይኖቻቸውን ጨፍነው ‹‹ቻው! ልጄ…እጄ እንጂ ልቤ መቼም አይጨክንብህም !›› ብለው እያለቀሱ ጨረሱት፡፡ በቀጣይዋ ጥይት የራሳቸውን ጭንቅላት በራሳቸው ጣት በተሳበ ቃታ አፈንድተው የልጃቸው ሬሳ ላይ ወደቁ ፡፡… ከተስፋዬ የወደድኩለት ጫወታ አዋቂነቱን ብቻ አይደለም፡፡ የርዕስ አመራረጡንም ጭምር እንጂ፡፡ የብዙዎቹ ታሪኮች ርዕስ እንደሚያስጎመዥ ማዕድ ፍላጎትን ያንራሉ፡፡ እንደገናም ደግሞ ከአእምሮ ይቀራሉ፤ ለአፍ ይቀላሉ፡፡ ‹ የጢቢኛ ፍቅር›፣ ‹አወይ ቀላድ አምባ› ፣‹የድድ ማስጫ ልጆች›፣‹ዱርዬው ባንድ› የሚሉት እና ሌሎችም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች ለዘለቄታው ከአእምሮ ውስጥ እንዳይጠፉ ተደርገው በደራሲው ብዕር ተከትበዋል፡፡

ደራሲው መግቢያ አጻጻፍ፣ ምስጋና መዘርዝር ላይ አዲስ ዘዬን ለመከተል የሞከረበትን መንገድ ግን ብዙም አልወደድኩለትም፡፡ ቀጥታ ወደ ታሪኮቹ ቢዘልቅ አልኩኝ፡፡ የ‹‹መንጌ ውሽሚት›› የሚለው ታሪክ የመጽሐፉ መጠሪያ እስከሆነ ድረስ ልቦለድ ይሁን ታሪክ ቀመስ ትርክት ቁርጡን ቢነግረን መልካም ነበር፡፡ መፅሐፉን ካነበቡ ወዳጆቼ ጋር ባደረግሁት ውይይት ‹‹ እውነተኛ ታሪክ ነው አይደለም” በሚል ብዙ ተሟግተናል፡፡ ደራሲው ሙግቱን የፈለገውና የፈቀደው ይመስላል። በመጨረሻም ይህንን መጽሐፍ የዚምባቡዌው ሰውዬአችን አንብበውት ይሆን ብዬ አሰብኩና ፈገግ አልኩኝ፡፡ ቸር እንሰንብት!

Published in ልብ-ወለድ

እዚህ ፍትህ ካጣን ወደ ዓለምአቀፉ ፍ/ቤት እንሄዳለን 20ሺ ሰው ሲፈናቀል አላውቅም ማለት ተቀባይነት የለውም በቅርቡ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሠማያዊ ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሠውን መፈናቀል አስመልክቶ ድርጊቱን በፈፀሙት የመንግስት ባለስልጣናት እና ተቋማት ላይ ክስ ለመመስረት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡ በዋናነት የክሡ መነሻ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የደረሠው መፈናቀል ይሁን እንጂ ከአመት በፊት በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ የደረሠው መፈናቀልና ያስከተለው ጉዳትም በክሡ እንደሚካተት ፓርቲዎቹ ተናግረዋል፡፡

ማስረጃዎችን አሠባስቦ በማቀናጀት ሃገር ውስጥ ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች ክስ በመመስረት በኩል ደግሞ የቀድሞው የቅንጅት አመራር አባልና በአሁን ሠአት ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባልነት ተገልለው በአለማቀፍ የህግ ባለሙያነት በመስራት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡ በክሱ አቀራረብና ባህሪ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያምን በቢሮአቸው አነጋግሯቸዋል፡፡ የክሡ ሂደት ምን ላይ ደረሠ? በሠማያዊ ፓርቲና በመኢአድ አነሣሽነት ነው ክሡ ሊመሠረት የታሠበው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ክሡ አልተጀመረም፡፡ ማስረጃ ሠብስበን ከተጐዱት ሠዎች የውክልና ስልጣን ወስደን ወደ ስራው እንገባለን፡፡

አሁን ግን ገና ነው፤ የውክልና ስልጣኑም አልተዘጋጀም፡፡ በአካባቢው ያሉ ሠዎችን ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ስራው አሁን በውል ተጀመረ ማለት ባይቻልም በቅርቡ ሠዎች ወደዚያው ሄደው የተጐዱና የተፈናቀሉ ሠዎችን በመጠየቅና የደረሠባቸውን ጉዳት በማየት መረጃ እያሠባሠቡ ነው፡፡ ክሡን የምንመሠርተው ከዚያ በኋላ ይሆናል ማለት ነው፡፡ መጀመሪያ እንደሚታወቀው መረጃውን ማሠባሠብ ያስፈልጋል፡፡ በግልፅ ህግ መጣሡን በደንብ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ከተሟሉ በኋላ በቀጥታ ወደ ክሡ እንሄዳለን፡፡ መጀመሪያ የሠዎቹን ውክልና ሣታገኙ እንዴት ለመክሠስ እየተዘጋጃችሁ መሆኑን ገለፃችሁ?

መጀመሪያ ውክልናውን ማግኘታችሁን ማረጋገጥ አልነበረባችሁም? እንግዲህ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዘን የምንቀርበው በሁለት አይነት ነው፡፡ የወንጀልም የፍትሃ ብሄር ጉዳይም አለው፡፡ የወንጀል ጉዳይን በተመለከተ ማንኛውም ሠው እንደተጐጂው ሆኖ ለፍትህ አካል አቤት ብሎ፣ ፖሊሶች ጉዳዩን ከመረመሩና ማስረጃውን ካጠናቀሩ በኋላ ወደ አቃቤ ህግ ይመሩታል፡፡ አቃቤ ህግ ክስ ይመሠርታል ወይንም በቂ ማስረጃ የለኝም፤ ክስ አልመሠርትም ብሎ ሊተወው ይችላል፡፡ በቂ ማስረጃ ካለ ደግሞ ክስ መስርቶ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በቀጥታ እኛ የምንሣተፍበት ደግሞ አለ። እነዚህ ሠዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል፤ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ የንብረት መውደም ደርሶባቸዋል፣ ጤናቸው ታውኳል፣ ብዙ አይነት ጉዳት ነው የገጠማቸው፡፡ ያ ሁሉ በገንዘብ ተሠልቶ የሚገባቸውን ካሣ፣ ተጠያቂ የመንግስት አካላት እንዲከፍሉ ነው የሚደረገው፡፡ መኢአድና ሠማያዊ ፓርቲ ከተጐጂዎች መካከል በርካቶቹን ጠይቀው ፈቃደኝነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የውክልና ስልጣን ከዚያ በኋላ ይመጣል ማለት ነው፡፡

ክሱ በዚህ አገር ያልተለመደ ዓይነት ይሆናል ብለው ነበር፡፡ ሊያብራሩት ይችላሉ? ብዙ ሠው የያዘ ቡድን አንድ አይነት ጉዳት ከደረሠበት አንዱ ብቻ ከሶ ፍርድ ካገኘ ሌሎቹም ክስ ሣይመሠርቱ ከውጤቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሄ በፈረንጆች “ክላስ አክሽን ሱት” ይባላል። ለምሣሌ የተፈናቀለው የአማራው ህብረተሠብ ተመሣሣይ በደል ነው የደረሠጁ እና ከእነሡ ውስጥ አንድ ሠው ብቻ ከሶ ፍርድ ካገኘ (ከረታ) ሌሎቹ የተጐዱ ሠዎች ክስ ሣይመሠርቱ፣ ለፍርድ ቤቱ ተመሣሣይ በደል እንደደረሠባቸው በማመልከት ብቻ ከፍርዱ እኩል ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ይህ በሃገራችን ብዙም አልተለመደም ግን እኛ ይህ አካሄድ በሃገራችን ይሠራል የሚለውን ልንፈትሸው ነው፡፡ ጉዳዩን በምሣሌ ማየት ይቻላል። አንድ መለያ ያለው የጥርስ ሣሙና ከገበያ ገዝተህ ሣሙናው የተመረዘ ቢሆንና ብዙ ሠዎች ተጠቅመውት ከተጐዱና አንድ ሠው ብቻ ክስ አቅርቦ ከኩባንያው ካሣ ካገኘ፣ ያንን የጥርስ ሣሙና ተጠቅመው ተጐጂ የሆኑ ሠዎች ከዚያ ፍርድ ውጤት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

እኛም በዚህ መልኩ ነው ክሣችንን የምንመሠርተው፡፡ በእያንዳንዱ ተጐጂ ስም ክስ የማቅረብ ሃሣቡ የለንም፡፡ ውክልናውን ከአንድ ሠው ብቻ ብታገኙም መክሠስ ትችላላችሁ ማለት ነው? አዎ በሚገባ ይቻላል፡፡ ውክልና የሠጠን ሠው ከፍርድ ሂደቱ በሚያገኘው ውጤት ተመሣሣይ ጉዳት ያጋጠማቸው ሁሉ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሠረት የአንድ ሠውም ውክልና የመንግስትን ተጠያቂ አካላት ለመክሠስ ያስችለናል፡፡ በአገራችን ይህን ለማድረግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ አለ?

በህገ መንግሥቱም አለ፣ በወንጀለኛ መቅጫውም በፍትሃ ብሄር ህጉም አለ፡፡ ለምሣሌ በህገ መንግስቱ ላይ “ክላስ አክሽን ሡት” የሚባለውን በተመለከተ የተጠቀሠ አለ፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 37 ላይ “ማንኛውም ቡድን ወይም ተመሣሣይ ጥቅም ያላቸውን ሠዎች የሚወክል ግለሠብ ወይም የቡድን አባል የመጠየቅና የማግኘት መብት አለው” ይላል፡፡ እንግዲህ ማንኛውም ግለሠብ፣ ተመሣሣይ ጥቅም ያላቸው የቡድን አባላትን ወክሎ የመጠየቅና የማግኘት መብት አለው፡፡ እንግዲህ ያ የሚወክለው ግለሠብ ጠበቃ ሊሆን ይችላል፡፡

የቡድኑ አባል ደግሞ ከተበዳዮች አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከተጐጂዎች ውክልና የሚሠጣችሁ ሠው ብታጡስ…ምን ታደርጋላችሁ? የተሠሩ ወንጀሎችን ከአንዳንድ ሠዎች ጠይቀን፣ ያንን ሪፖርት ለፖሊስ እናቀርባለን። ፖሊሶች ለአቃቤ ህግ ያቀርባሉ፡፡ አቃቤ ህግ መረጃና ማስረጃዎችን መዝኖ ክስ ይመሠርታል፡፡ በፍትሃብሄር ካሣ ለማግኘት ግን እነሡ የውክልና ስልጣን ካልሠጡን አይሆንም፡፡ የወንጀሉ ክስ ግን እነሡ ውክልናውን ቢሠጡም ባይሠጡም ይቻላል፡፡ እኛ ሣንሆን በወንጀሉ አቃቤ ህግ ነው የሚከሠው፡፡ እኛ ግን እስካሁን የተረዳነው፣ ሠዎች የዚህ የፍትሃብሄር ክስን በተመለከተ በመኢአድና በሠማያዊ ፓርቲ አማካኝነት ክሡን ለማቅረብ ፍላጐት እንዳላቸው ነው፡፡ ዋነኛ ማስረጃችሁ ሊሆን የሚችለው ምንድን ነው? ዋነኛ ማስረጃ የሚሆኑት ተጐጂዎቹ ራሣቸው ናቸው፡፡ ለምስክርነት ይቀርባሉ፡፡ የመንግስት ባለስልጣናትም ለምስክርነት ይቀርባሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሣለኝ ይሄ ነገር ከባድ ወንጀል እንደሆነና መፈፀም እንደሌለበት፤ በአጥፊዎች ላይም መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል፡፡ እሣቸውም በአካልም ሆነ ንግግራቸው በቪዲዮ ማስረጃነት ያለ ጥርጥር ይቀርባሉ፡፡ እርግጥ ማስረጃ በተለይ በተጐጂዎች ሲቀርብ የፍርሃቱ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ የክልሎቹ ባለስልጣናትም ሆኑ የፌደራሎቹ ሊያስፈራሯቸው ይችላሉ፡፡ ጥቃት የደረሠበት ሠው ደግሞ ይፈራል። አሁንም ጥቃት ውስጥ ያሉ ሠዎች ናቸውና ሊፈሩ ይችላሉ፡፡ ግን መኢአድና ሠማያዊ ፓርቲ እንዳረጋገጡልን በዚህ ጉዳይ ላይ ለመግፋት የሚፈልጉ ሠዎች አሉ፡፡ አንዱ የክሱ ጭብጥ “ዘር ማጥፋት” የሚል መሆኑን በሠጣችሁት መግለጫ ላይ ጠቅሳችኋል። ዘር ማጥፋት ሲባል ምንድን ነው? ዘር ማጥፋት በሚለው ክስ ለማቅረብ የሚያስችላችሁ የህግ ማዕቀፍ ይኖራል? ሁለት አይነት ወንጀሎች ናቸው፡፡ የዘር ማጥፋት የሚለው አንዱን ብሄረሠብ ወይም ዘር በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በማቀድ፣ በማሠብ ጥቃት መፈፀም ማለት ነው፡፡ ያን ጥቃት መፈፀም እንግዲህ ዘር ማጥፋት ሊሆን ይችላል። ዘር ማጥፋት (ዲፖርቴሽን) ሊሆን ይችላል፣ ማፈናቀልም ሊሆን ይችላል፣ ልጆች እንዳይወልዱና የዘር መተካካቱ እንዳይቀጥል ማድረግም ሊሆን ይችላል፡፡

ይሄ እንግዲህ በሠው ዘር ላይ የሚሠራ ወንጀል ነው - ጀኖሣይድ ወይም የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው። አሁን እኛ እንደምንገምተው አማሮችን ከየክልሉ የማባረሩና የማፈናቀሉ ነገር ቆይቷል፡፡ ከበደኖ ጀምሮ አርባጉጉ፣ ጉራፈርዳ አሁን ደግሞ ቤንሻንጉል… ሌሎችም አሉ፡፡ ይሄ ቢደረግም የአማራን ዘር በከፊልም ሆነ በሙሉ ለማጥፋት ታቅዶ የሚደረግ ነው ወይ ለሚለው ማስረጃ የለንም፡፡ እነዚህ ሠዎች ለመፈናቀላቸው ከቦታ ቦታ መነቀላቸው፣ ንብረታቸውን ማጣታቸው፣ በአካላቸው ላይ ጉዳት መድረሡን እናውቃለን፤ ማስረጃውም አለ። እንግዲህ የዘር ማጥፋት ሣይሆን የዘር ማጥፋት ወንጀል የምንለው ከነበሩበት አካባቢ በዘራቸው ምክንያት ከተፈናቀሉ ነው፡፡ አንድ ሠው በዘሩ፣ በሃይማኖቱ ወይም በሚናገረው ቋንቋ ምክንያት ጉዳት ከደረሠበት በሠው ዘር ላይ የሚሠራ ወንጀል ነው፡፡ አሁን ሠዎች በአማራነታቸው፣ በዘራቸው በተቀነባበረ መልክ ለብዙ ጊዜ የዘር ማጥፋት ወንጀል በዚህ መልኩ ተፈፅሞባቸዋል፡፡

በአካባቢው አንድ ዘር ብቻ እንዲኖር ካለ ፍላጎት፣ እነዚህ ዘሮች (አማሮች)ከሚኖሩበት ተፈናቅለዋል፡፡ እና ይሄ ዘር ማጥፋት ይባላል፡፡ ሁለተኛው የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚጀምረው አንድ ሠው በሃይማኖቱ፣ በዘሩ ምክንያት በተቀነባበረ መልኩ በሠፊው ግድያ፣ መፈናቀል፣ የመሣሠሉ ነገሮች ከተፈፀሙበት ነው። ሁለቱም በጣም ከባድ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በአለማቀፍ ህግ መሠረትም በተመሣሣይ የወንጀል ፈርጅ ነው የሚቀመጡት፡፡ ተመሣሣይ ቅጣት ያስከትላሉ፡፡ እኛ አሁን በኢትዮጵያ የተፈፀመው ወንጀል የዘር ማጥፋት ነው ብለን ደፍረን ባንወጣም፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይ በአማራዎች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ እኔ በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ የሚለውን አልቀበለውም፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም አማርኛ ተናጋሪዎች ነን፡፡ በዚህ መሠረት አማራዎች ለረጅም ጊዜያት በተቀነባበረ መልኩ ከተቀመጡበት ሲፈናቀሉ ኖረዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአለማቀፍ ህግም በሃገራችን የወንጀለኛ መቅጫ ህግም ወንጀል ነው፡፡

“በዘር ማጥፋት” ወንጀል መክሠስ የሚያስችላችሁ የህግ ማዕቀፎች አሉ? በደንብ አሉ፡፡

አሁን እኔ እንዳጋጣሚ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉን አልያዝኩትም እንጂ ይሄን የሚቀጣ አንቀፅ አለ፡፡ እንደውም የደርግ ባለስልጣናት በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሠው ነበር፡፡ በእርግጥ ክሡ ትክክል ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ወንጀሉ ያነጣጠረው የፖለቲካ ቡድንን መሠረት አድርጐ ነበር፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል የምንለው በሃይማኖት፣ በቋንቋ እና በዘር ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በፖለቲካ እምነት መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ አንፃር በህጋችን የዘር ማጥፋት ምንድን ነው የሚለው በግልፅ ተቀምጧል፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል ማለት በሠው ዘር ላይ የሚፈፀም ወንጀል ወይም ማፈናቀል መሆኑ በህጋችን በግልፅ ተቀምጧል፡፡ የደርግ ባለስልጣናትም የተከሠሡት አንደኛ በዘር ማጥፋት፣ ሁለተኛ ደግሞ በዘር ማጥራት፣ ሶስተኛ ደግሞ በተራ ግድያ ተጠያቂ ሆነው ነበር፡፡ ጉዳዩ ከመሬት እና ከይዞታ ጋር የተገናኘ እንጂ የዘር ጥላቻ አይደለም የሚሉ አካላት አሉ? የዘር ጥላቻ ሆነም አልሆነም ዋናው ነገር መፈናቀላቸው ነው፡፡

ከቤት ንብረታቸው ብዙ ጊዜ የኖሩበትን ቦታ በግድ ማስለቀቅ ጥላቻ ቢኖረውም ባይኖረውም ወንጀል መሆኑ አይቀርም። በህገ መንግስቱ አንቀፅ 32፣ የመዘዋወር መብትን በተመለከተ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በህጋዊ መንገድ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሃገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሃገር የመውጣት ነፃነት አለው” ይላል፡፡ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም፤ ለውጭ ዜጐችም ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በፈለጉበት መኖርና ወደፈለጉበት መንቀሣቀስ ይችላሉ፡፡ ለውጭ ሃገር ሠዎች እንኳ መብቱ ተሠጥቷል፡፡ ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል ላይ መኖርና ሠርቶ መለወጥ ይችላል ማለት ነው፡፡ እርግጥ አንዳንድ የተከለሉ አካባቢዎች አሉ፡- እንደጦር ሠፈር፣ ቤተመንግስት፣ የእንስሣት ፓርኮች የመሣሠሉት … እዚያ ልግባ ቢሉም ልኑር ማለት አይቻልም፡፡ በተረፈ ግን ዘሩም ሆነ ቋንቋው ምንም ቢሆን የፈለገበት ቦታ ሄዶ የመኖር መብት እንዳለው ህገ መንግስቱ በግልፅ ይደነግጋል፡፡

አንድ ጊዜ ከጉራፈርዳ ስለተፈናቀሉ ሠዎች ጉዳይ በፓርላማው ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ጠ/ሚ መለስ በወቅቱ እነዚህ ሠዎች ደን ይመነጥሩ ነበር ብለው መልስ ሠጡ፡፡ የዚህ አንደምታው የተወሠደው እርምጃ ትክክል ነው የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሠዎች ዛፍ ይቆርጡ እንደሆነ ህግ ካለ በህግ ይጠየቃሉ፤ ጫካ ይመነጥሩ እንደሆነም እንደዚያው፡፡ አሁን አቶ ኃይለ ማርያም የተለየ መልስ ሰጥተዋል፡፡ አቶ መለስ ፍፁም ህጋዊ አድርገው የቆጠሩትን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ህገወጥ መሆኑንና መደረግ እንደሌለበት፤ መንግስትም እርምጃ እንደሚወስድ ገልፀዋል፡፡ ከአካባቢው አማራዎች ብቻ ሣይሆኑ ኦሮሞዎችም የመፈናቀል እጣ ገጥሟቸዋል ተብሏል።

ይሄንንስ እንዴት ነው የሚያዩት? በእርግጥ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ብለውታል፡፡ ነገር ግን በአማራዎች ላይ እየደረሰ ያለው መጠነ ሰፊ ነው፡፡ የቆየም ነው፡፡ በግብታዊነት ሰዎችን ማፈናቀል በፕላን የተሠራ የቆየ ድርጊት ነው። ሊፈፀም የማይገባው ወንጀል ነው የተፈፀመው፡፡ አሁን ክስ እንመሠርትባቸዋለን ከምትሏቸው ሃላፊዎች መካከል በህዝብ ተመርጠው የምክር ቤት አባላት የሆኑ አሉ፡፡ የእነዚህን ሰዎች ያለመከሰስ መብት ከግምት አስገብታችኋል? እንግዲህ አንድ የህዝብ ተወካይ ሊከሰስ የሚችለው ፓርላማው የዛን ሰው ያለመከሰስ መብት ሲሰርዝ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምናልባት እንደዚህ አይነት ያለመከሰስ መብት እንዳላቸውና እንደሌላቸው ማጣራት ይኖርብናል፡፡

ካላቸው ፓርላማ ወይም ምክር ቤት በዚህ በዚህ ወንጀል ምክንያት ያለመከሰስ መብታቸውን መሰረዝ አለበት ብለን ማመልከት አለብን፡፡ ያኔ ምክር ቤቱ ፍቃድ ከሰጠና ከሠረዘ ይከሰሳሉ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ሂደት ካልታለፈ መክሰስ አይቻልም። የትኛውም ፓርላማ እንዲህ አይነት ከባድና ግልጽ ወንጀል በሚፈፀምበት ጊዜ ያንን ያለመከሰስ መብትን ያሠርዛል፡፡ እኛም የትኛው ነው ያለመከሰስ መብት ያለው የሚለውን ካጣራን በኋላ፣ አስቀድመን ለምክር ቤቶቹ አመልክተን መብቱ እንዲሠረዝ እንጠይቃለን፡፡ ክሳችሁ የሚያካትተው በየትኛው ጊዜ እና በየትኛው የሃገሪቱ ክልል የተፈፀሙትን ወንጀሎች ነው? አሁን ለጊዜው ቤንሻንጉል እና ጉራፈርዳ የተከሰተውን ነው ያሰብነው፡፡ ሌላው በቀጠሩን ፓርቲዎች የሚወሰን ነው፡፡ በእርግጥ ድርጊቱ በብዙ ቦታዎች የተፈፀመ ነው፡፡ ግን ክስ የሚመሠረተው አንድም እንዲህ አይነት ድርጊት ለወደፊቱ እንዳይደገም ማስተማሪያ እንዲሆን ነው፡፡

ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆም ለማድረግ ነው፡፡ ክስ ብዙ ጊዜ የሚመሠረተው ከክሱ ውጤት ሌላው እንዲማርና ተበዳዩ እንዲካስ ነው፡፡ ክሱ በአገር ውስጥ ፍ/ቤቶች ተቀባይነት ካጣ ወደ አለማቀፍ ፍ/ቤት እንሄዳለን ብላችኋል፡፡ ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ፍርድ ቤት አባል ሳትሆን ክስ መመስረት ይቻላል? የክሱ አንዱና ዋናው አላማ ይህ ድርጊት ከእንግዲህ በማንም ኢትዮጵያዊ ላይ እንዳይፈፀም ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ይሄ ክስ እዚህ ሊሳካልን ባይችል በአለማቀፍ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ለነዚህ ኢትዮጵያውያን የዳበረ ማስረጃ ለመስጠት ነው፡፡ በአለማቀፍ ፍርድ ቤት ክስ ለመመስረት መጀመርያ የአገር ውስጡን ማጣራት አለብን፡፡ በአገር ውስጥ ፍትህ ከተነፈግን ወይንም የአገሩ መንግስት ሊሰማ ካልፈለገ ጉዳዩ ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ሊያመራ ይችላል፡፡ በፊት እንደተባለው ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ፍርድ ቤት አባል አይደለችም፡፡ ለምን እንዳልሆነች እኔ በእውነት ሊገባኝ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከአፄ ኃይለስላሴ ጀምሮ በደርግም ዘመን ኢትዮጵያ አለማቀፍ ስምምነቶችን በመቀበል ንቁ ተሣትፎ ነበራት፡፡ የተባበሩት መንግስታትን ቻርተር ለመፈረም እኮ የመጀመሪያዎቹ ጥቁር ህዝቦች እኛ ነን፡፡

ኢህአዴግ ለምን ሊቀበለው እንዳልፈለገ አይገባኝም፡፡ ሆኖም ግን አገር ውስጥ ከባድ ወንጀል በሚፈፀምበት ጊዜ አባል አይደለችም፤ ስለዚህ አትከሰስም ተብሎ አይታለፍም፡፡ አባል ከሆነ በቀጥታ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ እንዲመረመር ያዛል፤ ተመርምሮ ክስ ይቀርብበታል። እንደ ኢትዮጵያ የፍርድ ቤቱ አባል ካልሆነ፣ ጉዳዩ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክር ቤት ቀርቦ፣ የፀጥታው ምክር ቤት ፍርድ ቤቱ ምርመራ እንዲያደርግና ክስ እንዲመሠርት ሊያደርግ ይችላል፡፡ አሁን ኢትዮጵያኖች የሚንቀሳቀሱበት መንገድ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ እጁን ያስገባና የአለማቀፍ ፍርድ ቤትን ምርመራ እንዲያደርግ ያዛል (ክስ እንዲመሠረት ሊያዘው አይችልም) ጉዳዩ ወደ ወንጀል ከመራ፣ ክሱ በተጐጂዎች ወይም ወኪሎች ሊቀርብ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ፍርድ ቤት አባል አለመሆኗ፣ ወንጀል ከተሰራ ከክስ ሊያስመልጣት አይችልም፡፡ እዚህ ፍትህ አለመኖሩ ከተረጋገጠ፣ በዚህ መልኩ ወደ አለማቀፉ ፍርድ ቤት እንሄዳለን፡፡

ክሱን የምትመሠርቱት ግለሰብ ባለስልጣናት ላይ ነው ወይስ ተቋማቱን ነው የምትከሱት?

ለምሣሌ ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን እንደመስሪያ ቤት ነው ወይስ ሚኒስትሩን ነው? እኛ ተቋማቱን ነው የምንከሰው፡፡ እርግጥ ለተቋማቱ ተጠሪዎች አሉ፡፡ ተከሳሾች የሚሆኑት ደግሞ የክልል አስተዳዳሪዎች ብቻ አይደሉም። እንደውም ከፌደራል ጉዳይ መስሪያ ቤት ይጀምራል፡፡ እርግጥ አቶ ኃይለማርያም፤ ይሄ በኪራይ ሰብሳቢዎች፣ በሌቦች የተፈፀመ ነገር ነው፤ መንግስት አያውቀውም ብለው ነው መግለጫ የሰጡት፡፡ ይሄ ተአማኒነትና ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው፡፡ ሃያ ሺህ ሰው ሲባረር አላውቅም ማለት የማንን ጐፈሬ ሲያበጥሩ ነበር ያስብላል፡፡ ፌደራል መንግስት ማወቅ ነበረበት፤ ባያውቅም የግዴታ ማወቅ ነበረበት። አላወቅሁም ካለም አለማወቅ ከተጠያቂነት ስለማያድን ማወቅ ይገባው ነበር፡፡ ባያውቅ እንኳ ማወቅ ስለሚገባው በህግ ይጠየቃል። በዚህ መሠረት ክሳችን ከፌደራል መንግስት ይጀምራል፡፡ ወደ ክልል አስተዳደሮች ይሄዳል። ከዚያም ወደ ወረዳ፣ ፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ወደተነካኩት አካላት ይሄዳል፡፡

እንግዲህ ክሱ እንደገለጽኩት ገና አልተረቀቀም፤ በመነጋገርና መረጃ በማሰባሰብ ላይ ነው ያለነው፡፡ ሀገር ውስጥ ካሉት ፍርድ ቤቶች ምን ውጤት ትጠብቃላችሁ? የመጨረሻ ውጤቱስ ምን ይሆናል ብላችሁ ነው የምታስቡት? እኛ መቸም የምንጠብቀው ህጉ ይተገበራል ብለን ነው፡፡ የወንጀል ህጉም ሆነ ሌሎች ህጐች ይተገበራሉ ብለን ነው የምንጠብቀው፤ ግን የሚሆነው ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ክሳችንን ውድቅ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱን ተቀብሎ ካሣ የሚያስከፍል ወንጀል አላገኘንም ብሎ ክሱን ሊዘጋው ይችላል፡፡ ሆኖም ግን እኛ አስቀድሜ እንዳልኩት ይሄን ክስ ያነሳነው በአለማቀፍ ችሎት የቀረበ እንደሆነ፣ መጀመሪያ በሃገር ውስጥ ፍትህ ለማግኘት ተሞክሯል ወይ ተብሎ ስለሚጠየቅ ነው።

ፍትህ ለማግኘት ሞክሬ ፍትህ አላገኘሁም ወይም መንግስት ክሱን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም ካልክ፣ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሊቀበለው ይችላል፡፡ ለዚህ ድጋፍ እንዲሆን ነው ይህን ክስ የምንመሠርተው፡፡ በእውነት ፍትህ በሀገር ውስጥ አግኝተን ለእያንዳንዱ ካሣ ቢከፈል በጣም እገረማለሁ፤ እደነቃለሁ፡፡ ቢሆን ግን እሰየው ነው። ጉዳዩን እንዴት እንደሚያመልጡት አላውቅም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው በደል ተፈጽሟል፣ ህግ ተጥሷል ካሉ እንዲሁ ዝም ብሎ ተነግሮ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በደል ከተፈፀመ የግድ ለተበዳዩ የሚሆን ካሣ ይከተላል፡፡ ይሄ ሊሆን ግድ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ተጠያቂ ይሆኑበታል፡፡ ወንጀል መሆኑን እያወቁ፣ በደል መፈፀሙን እያመኑ ዝም ብለው ካለፉት፣ ነገ በራሳቸው ቃል ተጠያቂ ይሆኑበታል፡፡

ወንጀልን ለመከላከል በሚታጠቁት መሳሪያ የግድያ ወንጀል የሚፈፅሙ የፖሊስ አባላት በርካታ መሆናቸውንና በአዲስ አበባ ብቻ ባለፉት ሰባት አመታት ከእስር በላይ በፖሊስ አባላት የተፈፀሙ ግድያዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ፖሊስ በበኩሉ፣ አብዛኞቹ የፖሊስ አባላት ህግ ለማስከበር፣ ወንጀልን ለመከላከልና ፍትህን ለማስፈፀም ጠንክረው የሚሰሩ መሆናቸውን ገልፆ፣ የፖሊስን አቋም በተቃረነ ወንጀል የሚፈፅሙ አባላትን በአገሪቱ ህግ መሰረት ለፍ/ቤት በማቅረብ ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ መቆየቱን ይገልጻል፡፡ የፖሊስ አባላት ፅኑ የፍትህ አቋም እንዲኖራቸው፣ ሥነ ስርዓት አክባሪነታቸዉ እንዲጠናከር፣ እንዲሁም ሥነ ስርዓት የሚጥሱትም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የተለያዩ የመተዳደሪያ ደንቦች ተግባራዊ እየተደረጉ መቆየታቸውን ፖሊስ ይገልፃል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሥነ ስርዓት ደንቡን ይበልጥ ለማሻሻል የዲሲፕሊን መመሪያና የቅጣት አወሳሰን ሰነድ አዘጋጅቶ እንዳጠናቀቀ ተጠቁሟል፡፡ በባህር ዳር ያጋጠመውን አይነት አሰቃቂና አሳዛኝ ድርጊት ዳግመኛ እንዳይከሰት ለመከላከል፣ በፖሊስ አባላት የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችና የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ ውይይት እንዲፈጠር ለማበረታተት በማሰብ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከፖሊስና ከፍ/ቤት ያሰባሰብናቸውን መረጃዎች አቅርበናል፡፡ ከ2 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ተፈርዶባቸዋል ባልደረባውን በ18 ጥይት መትቶ የገደለው ፖሊስ ጉዳይ በፍ/ቤት እየታየ ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል የሆነው የ20 ዓመቱ ኮሎኔል አወል አብዱልቃድር መስከረም 13 ቀን 1999 ዓ.ም ቦሌ ክ/ከተማ ቀበሌ 15 ክልል አቶ ሚካኤል ተሻለ የተባለ ግለሰብን ከመኪናው ያስወረደው “ትላንት ዘበኛህ የቤት ሠራተኛህን ደብድቦ ከያዝነው በኋላ አምልጦናል፤ እንፈልገዋለን” በማለት ነው፡፡ ከፖሊስ በተገኘ መረጃ መሰረት፤ ከተወሰነ የንግግር ልውውጥ በኋላ ኮሎኔል አወል በታጠቀው ክላሺንኮቭ ጠብመንጃ ግለሰቡን ጭንቅላቱ ላይ በመምታት በመግደሉ በከባድ ሰው የመግደል ወንጀል ተከስሷል፡፡ ጉዳዩን የመረመረው ፍ/ቤትም ግንቦት 7 ቀን 1999 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ በይኗል፡፡

ኮሎኔል አለሙ አያኖ በጉለሌ ክ/ከተማ፣ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት፣ ተስፋዬ ታደለ የተባለ ግለሰብ “ወደ ህግ ቦታ አልሄድም” አለኝ በሚል ምክንያት ለስራ በተሰጠው ክላሽንኮቭ ጀርባው ላይ በመምታት ስለገደለው ተከሶ ፍ/ቤት የቀረበው በጥር 2000 ዓ.ም ነበር፡፡ ሰኔ 18 ቀን 2000 ዓ.ም ፍ/ቤቱ በዋለው ችሎት ተከሳሹ በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣና ለሁለት ዓመት ከህዝባዊ ጥቅማጥቅም እንዲታገድ ወስኗል፡፡ የ23 ዓመቱ ኮንስታብል ሱልጣን ጀማል አሁን የሚገኘው ወህኒ ቤት ነው፡፡ የዛሬ ሰባት ዓመት ከስራ ባልደረባው ኰንስታብል አንሰ ሼህ አብደላ ጋር በተፈጠረ ጊዜያዊ ጠብ ምክንያት ለጥበቃ ሥራ በተሰጠው ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ግለሰቡን ተኩሶ በመግደሉ ፍ/ቤት በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡ የፌደራል ፖሊስ አባል የሆነው የ34 ዓመቱ ምክትል ሳጅን ደበሽ ታረቀኝም ወህኒ የገባው የስራ ባልደረባውን መግደሉ በፍ/ቤት ተረጋግጦበት ነው፡፡

ግለሰቡ፤ ኮንስታብል መሶር ዊይሰን የተባለውን ባልደረባውን አድርጐት በነበረው የወታደር ከስክስ ጫማ ጭንቅላቱ ላይ በመምታትና በመርገጥ ጉዳት ያደረሰበት መስከረም 17 ቀን 2000 ዓ.ም ሲሆን ለጥቂት ቀናት ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡ ፍ/ቤቱ የካቲት 13 ቀን 2001 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹ በ6 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ በይኖበታል፡፡ የፌደራል ፖሊስ አባሉ ኮሎኔል ኡፋይሳ ጉንዲስ ሐምሌ 3 ቀን 2004 ዓ.ም እስራኤል ኤምባሲ አካባቢ በጥበቃ ላይ የነበረውን ባልደረባውን በ18 ጥይት መትቶ በመግደል ተጠርጥሮ ክስ የተመሰረተበት ሲሆን ጉዳዩ በፍ/ቤት በመታየት ላይ እንደሚገኝ ከፖሊስ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ኮሎኔል ብዟየሁ ግርማም፤ “ሰው በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ ጉዳዩ በፍ/ቤት እየታየ ይገኛል፡፡ ኮሎኔሉ ሌሊት በሥራ ላይ እያለ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ በመጓዝ ላይ ያለ የነበረ ሚኒባስን እንዲቆም ይጠይቃል፡፡ ሹፌሩ መኪናውን ለማቆም በማቀዝቀዝ ላይ ሳለ ኮሎኔሉ ባልታወቀ ምክንያት ተኩስ በመክፈቱ የሚኒባሱ ሹፌር ህይወት ማለፉን የክስ መዝገቡ ያመለክታል፡፡

ኮሎኔል ብዟየሁ በተጠረጠረበት የሰው መግደል ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ ሲሆን ድርጊቱን መፈፀሙን እንዳመነ የፖሊስ መረጃ ይጠቁማል፡፡ “ድርጊቱን የፈፀምኩት ሰይጣን አሳስቶኝ ነው” ብሏል - ለፍ/ቤት በሰጠው ቃል፡፡ የ22 ዓመቱ ኮሎኔል ሃብታሙ ካሣሁን ጌታሁን፤ እስር ቤት የገባው በግድያ ሳይሆን በዘረፋ ወንጀል ተከሶ ነው፡፡ መስከረም 12 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ በ9 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ዑመር ስመትር ት/ቤት አካባቢ ወ/ት ዘሃራ አብዱራህማንን በያዘው ሽጉጥ ሰደፍ ቀኝ ጉንጯ ላይ በመምታት ከጣላት በኋላ፣ ከቦርሳዋ ውስጥ 1.514566.55 የያዙ የባንክ ቼኮች እንዲሁም 755 ብር የሚያወጡ ልዩ ልዩ እቃዎች ወስዶ ሊያመልጥ ሲል እጅ ከፍንጅ ይያዛል፡፡ በፈፀመው ከባድ የውንብድና ወንጀል የተከሰሰው ግለሰቡ፤ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ፍ/ቤት በ12 ዓመት ፅኑ እስራትና በ2ሺ ብር እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ኮሎኔል እዮብ ቀልሜሳ የዛሬ አራት ዓመት ሦስት የሥራ ባልደረቦቹ ላይ 18 ጥይቶችን በመተኮስ በፈፀመው የግድያ ሙከራ ተከስሶ ፍ/ቤቱ ጥፋተኝነቱን በማረጋገጡ ነው ወህኒ የወረደው - የ10 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበት፡፡ በእርግጥ ከዚህ ቀደምም ታስሮ ተፈቷል፡፡ በ1999 ዓ.ም በአደገኛ ቦዘኔነታቸው ከሚታወቁ ሁለት አባሪዎች ጋር ከሌሊቱ 6፡30 ላይ አንድ ግሮሰሪ ገብቶ ከአስተናጋጅ ላይ ገንዘብ በመውሰድና እቃዎችን በመሰባበር ክስ ተመስርቶበት ታስሮ ነበር፡፡ ከተፈታ በኋላ አንድ የስራ ባልደረባው በስብሰባ ላይ “ስራህ በሙሉ ከአንድ ፖሊስ የሚጠበቅ አይደለም፤ ሁልጊዜ እየታሰርክ ትፈታለህ፣ ከወንጀለኛ ጋር ነው የምትውለው” በማለት ከመጥፎ ምግባሩ እንዲመለሰ ይገመግመዋል፡፡ ኮሎኔል እዮብ ግን በስራው ከመፀፀት ይልቅ ቂም ይይዛል፡፡

ስብሰባው ሲጠናቀቅም “ለምሳ ተረኛ የግቢ ጥበቃ ነኝ” በማለት ክላሽንኮቭ ጠብመንጃና 30 ጥይት በመረከብ የገመገመውን ባልደረባውን ጨምሮ ሦስት የስራ ባልደረቦቹ ላይ 18 ጥይቶች በመተኮስ በፈፀመው የግድያ ሙከራ ተከስሶ ጥቅምት 4 ቀን 2001 ዓ.ም በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እና በሁለት ዓመት ከህዝባዊ መብት እንዲታገድ ተወስኖበታል፡፡ የ25 ዓመቱ ረዳት ሳጅን አስሬ አየለ ባይዴ፤ ባለፈው ዓመት አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ለማዋል ከ20 በላይ የፖሊስ አባላት ጋር በመሆን ወደ መኖርያ ቤቱ ይሄዳል፡፡ ተፈላጊው እጁን ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ፖሊሶች አጥር ዘለው ይገባሉ፡፡ ይሄኔ ግለሰቡ የፖሊስ አባላቱ ላይ ድንጋይ፣ ብርጭቆና ስለት መወርወር ይጀምራል፡፡ ረዳት ሳጅን አስሬ የፖሊስ ሙያ የሚጠይቀውን ጥበብ በመጠቀም ተጠርጣሪውን መያዝ ሲገባው በያዘው ክላሽ ጠብመንጃ ግለሰቡ ላይ በመተኮስ አንገቱ ላይ ይመታውና ወዲያው ህይወቱ ያልፋል፡፡

ሳጅን አስሬ አየለ ባይዴ፤ ህጋዊ መከላከልን ከመጠን በማሳለፍ በፈፀመው የግድያ ወንጀል ተከስሶ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ፍ/ቤት በሁለት ዓመት ቀላል እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡ ከፖሊስ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የፖሊስ አባላት በተለያዩ የግልና ሌሎች ያልታወቁ ችግሮች የተነሳ ራሳቸውን የሚያጠፉበት አጋጣሚዎችም አሉ - ብዙ ነው ባይባልም፡፡ በ1998 ዓ.ም አንድ ኮንስታብል በሚያድርበት ካምፕ ውስጥ በራሱ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ደረቱ ላይ ሁለት ጊዜ በመተኮስ እራሱን በራሱ ያጠፉ ሲሆን በ2000 ዓ.ም ደግሞ በብሄራዊ ቤተመንግስት በጥበቃ ሥራ ላይ ተመድቦ የነበረ አንድ ምክትል ሥራ ላይ ተመድቦ የነበረ አንድ ምክትል የአስር አለቃ በራሱ መሳሪያ አንገቱ ሥር በመተኮስ ራሱን በራሱ አጥፍቷል-ከፖሊስ በተገኘ መረጃ፡፡

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዋና ቅርንጫፎችን በስራ አስኪያጅነትና በህግ ክፍል ሃላፊነት ሲመሩ የነበሩ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ በዋስ ለመለቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አጣ፡፡ ዋና ዋና የንግድ መተላለፊያ ቅርንጫፎችን ሲመሩ የነበሩ ሁለት ስራ አስኪያጆችና ወንጀለኞችን የመክሰስ ሃላፊነት የተሰጣቸዉ ሁለት የህግ ክፍል ባለስልጣናት እንዲሁም ሌሎች ሃላፊዎችና ሰራተኞች በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩት ሰሞኑን ነው፡፡ ገሚሶቹ ከውጭ የመጡ እቃዎች ሳይቀረጡ እንዲገቡ አድርገዋል ተብለው የታሰሩ ሲሆን፤ ገሚሶቹ ደግሞ ቀደም ሲል የተከሰሱ ሰዎችን አላግባብ ከክስ ነፃ እንዲሆኑ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ናቸው፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራውን ለማጠናቀቅና በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ለመመስረት የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ጠይቆ የሁለት ሳምንት ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ግን ተቀባይነት ስላላገኘ፣ በእስር እንዲቆዩ ፍ/ቤቱ አዟል፡፡ በዚህ ሳምንት ታስረው በአዲስ የምርመራ መዝገብ ፍ/ቤት የቀረቡት 11 ተጠርጣሪዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ አቶ አምባውሰገድ አብርሃ፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የናዝሬት ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የህግ ማስከበር ሃላፊ አቶ ተክለአብ ዘርአብሩክ፣ የሚሌ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ያዴሳ ሚደቅሳ፣ የአዳማ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ግረፍ፣ የሚሌ ቅርንጫፍ የህግ ማስከበር ሃላፊ አቶ ጌታሁን ቱጂ፣ የአዳማ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሃላፊ አቶ መባኩ ግርማ፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ትራንዚት ኤክስፐርት አቶ አስፋው ስዩም፣ የድሬደዋ ቅርንጫፍ ላጋር ጉምሩክ መቅረጥ አስተባባሪ አቶ ጌታነህ ግደይ፣ የአቃቂ ቃሊቲ የመጋዘን ቡድን ሰራተኛ አቶ ዮሴፍ አዳዩ፣

የአቃቂ ቅርንጫፍ ሰራተኛ አቶ በእግዚያብሄር አለበል፣ የአልትሜት ፕላን የግል ድርጅት ከፍተኛ ባለድርሻና አማካሪ አርክቴክት አቶ ዘለቀ ልየው፣ የበምጫ ትራንዚት ባለቤት ናቸው፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው መከራከሪያ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት እስካሁን ያከናወነውን ስራ ዘርዝሯል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ቃላቸውን እንደተቀበለ ኮሚሽኑ ጠቅሶ፣ በበቂ ሁኔታ የሰነድ ማስረጃ ሰብስበናል፣ የምስክሮችን ቃል መቀበል ጀምረናል ብሏል፡፡ ከምርመራው ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ከየመስሪያ ቤቱ እያሰባሰበ መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቁሞ፣ ሰነዶችን ማደራጀትና የአይን እማኞችን ቃል መቀበል እንደጀመረ ገልጿል፡፡ የምርመራ ስራዎች እንደተጠናቀቁና የተጠርጣሪዎቹ ድርጊት በትብብር የተፈፀመ በመሆኑ፣ በርካታ ምርመራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልገው በመዘርዘር፣ ፍርድ ቤቱ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲፈቅድለት ኮሚሽኑ ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በቂ ማስረጃ መሰብሰቡንና የቀሩትም ቢሆን እነሱ ሊያጠፏቸው የማይችሉ እንደሆነ በማመልከት በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ በመስሪያ ቤት ያሉ ሰነዶችን እኔ ላጠፋቸው አልችልም ያሉት አቶ አምባውሰገድ አብርሃ፤ ከዚህ በተጨማሪም የልብ ታማሚ መሆናቸውን በመግለፅ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ ሁለተኛ ተጠርጣሪም ሰነዶች በሙሉ ተበርብረው መወሰዳቸውን ጠቅሰው፤ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሌሎች ተጠርጣሪዎችም የሰነድም ሆነ ሌሎች ማስረጃዎችን ለመደበቅና ለማሸሽ የሚያስችል ስልጣንና የኢኮኖሚ አቅም እንደሌላቸው ጠቅሰው የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ አመልክተዋል፡፡ 10ኛ ተከሳሽ አቶ በእግዚያብሄር አለበል፤ ከ60 በላይ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በአማካሪነት እንደሚያከናውኑ ገልፀው፣ ከገቢዎች እና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ጋር የሚያገናኘኝ ጉዳይ የለም በማለት፣ ፍርድ ቤቱ የዋስ መብታቸውን ይፈቅድላቸው ዘንድ ጠይቀዋል፡፡

11ኛ ተጠርጣሪ በጠበቃቸው በኩል ባቀረቡት አስተያየት፤ ከተያዙ ስድስት ቀን ቢሆናቸውም ፍርድ ቤት እስከቀረቡበት ቀን ድረስ ቃላቸውን እንዳልሰጡ፣ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ጋር ተያያዥነት የሌላቸው ሰነዶች መወሰዳቸውን እንዲሁም ቢሮአቸው እንደታሸገ እንደሚገኝ በማመልከት፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተጠርጣሪው በግላቸው ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ቃልም፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከአንድ ጊዜ በስተቀር አለመገናኘታቸውን የገለፁ ሲሆን በቢሮአቸው የነበረ ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ የተወሰደ በመሆኑ ከተወሰደው ገንዘብ ላይ ለልጃቸው የወተት መግዣ አንድ ሺህ ብር ብቻ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በበኩሉ፣ ማስረጃዎችን መሰብሰብ ጀምረናል አልን እንጂ በተሟላ መልኩ ሰብስበናል አላልንም፤ ብሏል፡፡

ከወንጀሉ ከባድነት አንፃር፣ ማስረጃዎች ተሰብስበው ካለመጠናቀቃቸው በተጨማሪ ተጠርጣሪዎቹ ሊጠፉ ስለሚችሉ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ መሆን አለበት ብሎ ተከራክሯል፡፡ ፍርድ ቤቱም በሰጠው ትዕዛዝ፤ የምርመራውን ውስብስብ ሂደት በመረዳት የ14 ቀን ቀጠሮ ፈቅዶ፣ ተጠርጣሪዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ከቀረቡበት ቀን ጀምሮ በሚታሠብ ለግንቦት 26 ቀን ቀጠሮ ሠጥቷል፡፡ ተጠርጣሪዎች ከቤተሠቦቻቸውና ከጠበቆቻቸው ጋር የመገናኘት መብት እንዳላቸው ፍ/ቤቱ ጠቅሶ፤ መብታቸው መከበሩን የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲከታተል አዟል፡፡

የተጠርጣሪዎች መብትን በሚመለከት ዝርዝር ሪፖርት እንዲቀርብለትም ፍ/ቤት ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ እሽግ ይነሣልኝ የሚለው ጥያቄ አስተዳደራዊ ምላሽ ይሰጥበት ያለው ችሎት፤ ቀለብ ማጣት ስለማይገባ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሣው ጥያቄም አስተዳደራዊ ምላሽ እንዲሠጥበትና በቀጣይ ቀጠሮ ሪፖርት እንዲቀርብበት አዟል፡፡ በሌላ በኩል በእነ አቶ መላኩ ፋንታ መዝገብ ስር በ5ኛ ተጠርጣሪ የኬኬ ኃ.የተ.የግ.ኩባንያ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ የቀረበውን የቢሮ እሽግ ይነሣልኝ ጥያቄን በተመለከተ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በእሽጉ ላይ አስተያየቱን እንዲሠጥበት ለግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡

Published in ዜና
Page 3 of 14