Monday, 11 May 2015 09:02

የፍቅር ጥግ

ከሁሉም ጣፋጩ ድምፅ ያፈቀርናት ሴት ድምፅ ነው፡፡
ዣን ዲላ ብሩዬር
የመጀመሪያ ዕይታዬ የሚያርፈው በልብሽ ላይ ነው፡፡
ጆሃን ኤፍ ሲ ሺለር
አበባ ያለ ፀሐይ ብርሃን እንደማያብበው ሁሉ፣ ሰውም ያለ ፍቅር መኖር አይችልም፡፡
ማክስ ሙለር
ለዓለም አንድ ሰው ነሽ፤ ለእኔ ግን ዓለሜ ነሽ፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
አፍቅሪኝ፤ ያኔ ዓለም በሙሉ የእኔ ትሆናለች።
ዴቪድ ሪድ
አንድ ቃል ከህይወት ሸክምና ስቃይ ነፃ ያወጣናል፡፡ ያ ቃል “ፍቅር” ነው፡፡
ሶቅራጦስ
ህይወትን ውደዳት፤ ህይወት መልሳ ትወድሃለች፡፡ ሰዎችን ውደዳ    ቸው፤ እነሱም መልሰው

ይወዱሃል፡፡
አርተር ሩቢንስቴይን
መሳሳም ጨዋማ ውሃ እንደ መጠጣት ነው። በጠጣህ ቁጥር ጥምህ ይጨምራል፡፡
የቻይናውያን አባባል
ስሞሽ (Kissing) የፍቅር ፊርማ አይደለምን?
ሔነሪ ፊንክ
ደስተኛ ትዳር ያፈቀርነውን ስናገባ ይጀምራል፤ ያገባነውን ስናፈቅር ደግሞ ያብባል፡፡
ቶም ሙሌን
የደስታን ሙሉ ጣዕም ለማግኘት፣  የምታካፍሉት ሰው ሊኖራችሁ ይገባል፡፡
ማርክ ትዌይን
በጣቶቻችሁ መካከል ያሉት ክፍት ቦታዎች የተፈጠሩት በሌሎች ጣቶች እንዲሞሉ ነው፡፡
ማንነቱ ያልታወቀ ፀሐፊ
በህይወት ውስጥ አንድ ደስታ ብቻ ነው ያለው፡፡ ይኸውም ማፍቀርና መፈቀር ነው፡፡
ጆርጅ ሳንድስ
መውደድን የምንማረው በመውደድ ብቻ ነው፡፡
አይሪስ ሙርዶክ
ፍቅር ሰዎችን ይፈውሳል - ሰጪውንም ተቀባዩንም፡፡
ካርል ኤ. ሜኒንገር
ጥላቻ በጥላቻ አይሻርም፤ በፍቅር ብቻ እንጂ፡፡ ይሄ ዘላለማዊ ህግ ነው፡፡
ቡድሃ
በፍቅር ለሚወድቁ ሰዎች ስበት ተጠያቂ አይደለም፡፡
አልበርት አንስታይን
ፍቅር ህይወት ነው፡፡ ፍቅር ካመለጠህ፣ ህይወትም ያመልጥሃል፡፡
ሊዮ ቡስካግልያ

Published in ጥበብ
Monday, 11 May 2015 08:55

መርዶ ባደባባይ

በአገራችን ባህል እኛ የምናውቀው፡-
    በሌሊት ነበረ ሰው ለቅሶ ‘ሚያረዳው,
    ተረጂው ሳይሰማ፣ በምስጢር ተይዞ ጎረቤት መክሮበት
    ለዚሁ እሚመጥን አንጋፋ ተመርጦ ዕድር ያመነበት፤
    በሥርዓት ነበር፣ ሰው መርዶ እሚረዳው
    ሃዘንተኛም ሰምቶ በወጉ ነበረ እርሙን የሚያወጣው፡፡
        ዛሬ ወግ ተሸሮ፣ ባህል ተሸርሽሮ
        ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ገኖ በዕድገት ተስፈንጥሮ
        እርም ባደባባይ ኦን-ላይን አወጣን
        የሟቾችን ሲቃ በፌስ ቡክ እያየን፡፡
        በዕድገት ኋላ ቀርተን፣ በመከራ ቀድመን
        በዘመን ተሳቀን፣ ዓለም ተሳልቆብን
        እንደ ሰው ተፈጥረን፣ አጉል ሞት እየሞትን
        በጉደኛው ዘመን እንደጉድ እየኖርን
        ይሄው ለዚህ በቃን! ይኸው ለዚህ ደረስን!!
    የጉድ ቀን አይመሽም፣ ፍርጃ እቤት አይውልም
    መከራ ሲመክር አስተዋይ አዕምሮ ቀና ልብ የለውም፣
    አገር መርዶ አረዳች፣ አገር እርም አወጣች በጠራራ ፀሐይ
    ሰቆቃ ዘነበ … በረዶ ወረደ … በአገሬ ሰማይ ላይ
    ህዝቡ ደረት ጣለ፣ ሳር ቅጠሉ አዘነ በእንባ ተጥለቅልቆ
    ሀዘን ቅጡን አጣ፤ ከል ለበሰ አገር ባንዲራ አዘቅዝቆ
    ድህነት በፊናው፣ ያሰበው ሞላለት ኮራ ግዳይ ጥሎ
    በወገን ደም ግብር የሱ ቆሌ ረካ፣ የእኛ ፅዋ ጎድሎ፡፡
***
    “ድህነት ወንጀል አይደለም” ይላል አዳሜ እንደዋዛ
    ከወንጀል-ወንጀልም እንጂ ጣጣ መዘዙ የበዛ፡፡
    ማጣት የሃጢያት ሥር ነው፣ የገዛ እርምን ያበላል
    የሰው ፊት የቋያ እሳት ነው፣ ከሩቁ ይለበልባል
    “ችግር በቅቤ ያስበላል”፣ ይሉት የአበሻ ጅል ተረት
    የስላቅ የፌዝ - መርፌ ነው፣ የነፍስ ግርዛት ሸለፈት
    አጅሬ ችግር ዱር አውሬ እንኳንስ ቅቤ ሊያበላ
    አየነው ለጉድ ተፈጥረን፣ በካራ አንገት ሲያስቀላ፡፡
    የድህነትን ጅብ ሸሽቶ - ቢወጣ ካገር ተሰዶ
    ጥርሶቹን ስሎ ጠበቀው፣ አይምሬው የባህር ዘንዶ፡፡
    ምስካየ ሕዙናን ነበርን፣ ለተሰደዱት አለኝታ
    ለሰቅጣጭ “የርድ” ሞት በቃን፣ አቤቱ የማታ ማታ!
    ፅናቱን ይስጥሽ አገሬ፣ ይከብዳል መርዶው የልጅ ሞት
        በተለይ እጅሽ አጥሮበት
        ሪቅሽ እየራቀበት
        ሌማትሽ ሲራቆትበት…
        የኑሮ ሚዛን ተዛብቶ
        በቀየሽ ልጅነት ጎልቶ …
    … ቢጨንቀው ስደትን መርጦ …
    ሲኳትን በረሃ አቋርጦ …
    በባዕድ ቀላድ ቀላውጦ …
    ተስፋውን ሊወልድ አምጦ!
    ካቀደው ሳይደርስ ምኞቱ
    በሰደፍ ሲቀላ አንገቱ
        ይከብዳል ለእናት ስሱ አንጀት
        ይዳብስሽ አምላክ በምህረት!
    ፅናቱን ይስጥሽ ኢትዮጵያ! ያድንሽ ከዳግም ውርደት
    በብልፅግና ፅደቂ! ገሃነም ይውረድ ድህነት!
    ገናናነትሽ ይመለስ - አይታይ ክብርሽ ኮስሶ
        ጥቃት አንገት ያስደፋል!
        ማጣት አንገት ያስቀላል!
        ይመራል ልክ እንደ ኮሶ!
    የሐዘን ማቅሽ ይቀደድ! ያቁምሽ በፈውሱ ማማ
    ሙሾ ወረዳው አብቅቶ - ህዳሴሽ በዓለም ይስማ!!
ደመቀ ወልዴ
22/08/2007 (በሊቢያ በሥደት ሳሉ
አይኤስአይኤስ በተባለ ቡድን በግፍ ለታረዱ ወገኖቻችን)

Published in ጥበብ

በአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሩሲያ ማኅበረሰብ በመላ አገሪቱ ለውጥ ለማምጣትና አርሶ አደሮችን ከገባርነት ሥርዓት ለማላቀቅ በተነሳሳበት ወቅት ስለማህበራዊ ለውጥ የሚያስረዳ አብዮታዊ ንድፈ ሐሳብ ያፈለቀው ተራማጁ ደራሲ አሌክሳንደር ኒኮላር ቪች ራዲሼቭ ነው፡፡ የራዲሼቭ ሕይወት ከሩሲያ ጭሰኛ ጋር የተያያዘም ነው፡፡ ለዚህም ነው በመላ የሕይወት ዘመኑ የሩሲያን ገባሮች ነጻ ለማውጣት ሲታገል የኖረው፡፡ ከዚህም የተነሳ ራዲሼቭ “አብዮተኛና ደራሲ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ታላቅ ደራሲና አብዮተኛ፤ የሩሲያ ገዥ መደቦች የድሀውን ህዝብ ተጋድሎ፣ የትውልዱን አበሳ መገንዘብ አለባቸው ብሎ የጻፈው ግጥም ታዋቂነትንና ህዝባዊ ከበሬታን አስገኝቶለታል፡፡
የግጥሙ ርእስ “ዋናው ችግራችን” የሚል ነው፡፡
“ብርዱ ሆዴ ገብቶ እያንጠረጠረኝ፣
እስከ አጥንቴ ዘልቆ እየቀዘቀዘኝ፣
አእምሮዬን ጠልቆ እያኮማተረኝ፣
ሲያውቀው ልቦናዬ በእሥር ላይ እንዳለሁ፣
ንጉሠ - ነገሥቴ ለዘአለዓለም ይኑር ብዬ እዘምራለሁ።
የሬሳዬን ሣጥን እኔው ተሸክሜ፣
እሰግድለታለሁ ሥልጣንን በዘሩ ለአገኘው ወንድሜ።
በብረት ሰንሰለት ታስሯል እጅ እግራችን፣
ከገባን ይኸው ነው ዋናው ችግራችን፡፡”
እ.ኤ.አ በ1917 ታላቁን የጥቅምት ሶሻሊስት አብዮት የመራው ቭላድሚር ኢሊች ሌኒን ለራዲሼቭና ለሌሎች ተራማጆች ታላቅ ከበሬታ ስለነበረው “ታላላቅ ሩሲያውያን የኩራት ምንጮቻችን ናቸው” ብሎ በጻፈው ሐተታ የራዲሼቭን ስም እየደጋገመ አንሥቶታል፡፡ “ታላላቆቻችን ብሄራዊ ጭቆናን ለማጥፋትና የምታምረውን ሀገራችንን ወደፊት ለማራመድ ከካፒታሊስቶችና ከመሬት ከበርቴዎች ጋር የአካሄዱት ተጋድሎ ታይቶኛል፡፡ ተሰምቶኛል፡፡ በእነርሱ እንድንኮራባቸው የአደረገንም ከገዥዎች ጋር የገጠሙት ክርክርና የአካሄዱት መራራ ትግል በእኛ ዘንድ በአርአያነቱ ታይቶ ለመስዋዕትነት ስለጠራን ነው፡፡ ከታላላቆቹ ሰዎቻችን ውስጥ ደግሞ
አንደኛው ራዲሼቭ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ታህሣሣውያን በ1870ዎቹ ዓመታት ላይ የተነሱት አብዮታውያን ናቸው፡፡ የሩሲያ ሰራተኛ ህዝብ እ.ኤ.አ በ1905 የብዙኃኑን አብዮታዊ ፓርቲ ሊመሰርትና ጳጳሳትንና የመሬት ባለሀብቶቹን የበላይነት ሊያጠፋ የቻለው እንደራዲሼቭ የመሳሰሉ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች አስቀድመው በአደረጉት ተጋድሎና በከፈሉት ዋጋ ነው” ብሎዋል፡፡ ሌኒን በዚህ ጽሑፉ፤ ራዴሼቭ በሩሲያ ታሪክ ከፍተኛ ቦታ ያለው መሆኑንም ተናግሯል፡፡ ተመራማሪው፣ ፈላስፋውና ገጣሚው አሌክሳንድር ኒኮላየቪች ራዲሼቭ የተወለደው እ.ኤ.አ ግንቦት 20 ቀን 1749 ነው፡፡ የቤተሰቡ ሐረግ ከባላባት ዘር የወረደ ሲሆን በተለይ በእናቱ በኩል ዘመዶቹ ሁሉ የባላባት ምሁራን ነበሩ፡፡ የወደፊቱ ደራሲ ራዲሼቭ ሰባት ዓመት ሲሞላው ከአገር ቤት ሞስኮ ውስጥ ወደ ሚኖሩት ዘመዶቹ አመጡት፡፡ በተለይም የተቀመጠባቸው አጎቱ ሚሃይል ኤፍ አርጋማኮቭ በጊዜው በተከፈተው የሞስኮ ዩኒቨርሲቲ ዲን ስለነበር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሆኑት
ከአጎቱ ልጆች ጋር ለመቀራረብና ብዙ ነገሮችን ለማወቅ ዕድሉን አገኘ፡፡ እ.ኤ.አ በ1762 ሞስኮ ቤተመንግስት ውስጥ በሚገኘውና ፓዥ ትምህርት ቤት ተብሎ በሚጠራው ገብቶ እንዲማር ሁኔታው ተመቻቸለት፡፡ ፓዥ ትምህርት ቤት በዳግማዊ የካቴሪና ስም የተሰየመና ጎበዝ ተማሪዎች የሚማሩበት የትምህርት ተቋም ነበር፡፡ ትምህርተ ቤቱ የሕግ ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ ለማጥናት የሚፈልጉ ተማሪዎችን ለመሰናዶ ይቀበል ነበር፡፡ በመጨረሻ በፓዥ ትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ያመጡ ወጣቶች ወደ ሊቴጌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት እንዲያጠኑ ሲላኩ ራዲሼቭም ተመርጦ ሄደ፡፡ ሊፒስጌ ዩኒቨርሲቲ ለአምስት ዓመታት ያህል (እ.ኤ.አ ከ17-66-1771) የህግ ትምህርት ከማጥናቱ ባሻገር የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሥነጽሑፍ፣ ፍልስፍናና ልዩ ልዩ የውጭ አገር ቋንቋዎችን ተምሯል፡፡ አስተሳሰቡን አተቡና በኪነ ጥበብና በፍልስፍና ላይ አተኮሩ፡፡ የፈረንሳይና የጀርመን መጻሕፍትንም ለማንበብና በጥልቀት ለመመርመር ዕድል አግኝቷል፡፡ በተለይም “የአስተሳሰብ ምጥቀት” የተሰኘው የሒሌርት መጽሐፍ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ተናግሯል፡፡ ነባራዊዋና ተጨባጭዋ ህይወትም ለራዲሼቭ ፍልስፍና ታላቅ እገዛ አድርጋለች፡፡ እርሱን ጨምሮ የሩሲያ ተማሪዎች በሊፒስጌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመማር ላይ እያሉ ዘለዓለማዊና መለኮታዊ ሥልጣን አለን ከሚሉት የሩሲያ ገዥ
መደቦችና ባለርስቶች ጋር ለመፋለም ቁርጠኛ ሐሳብ አደረባቸው፡፡ ራዲሼቭ ከሊፒጌስ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ከአጠናቀቀ በኋላ እርሱና ጓደኞቹ በተማሩት የህግ ትምህርት መሠረት ለሀገራቸውና ለህዝባቸው አገልግሎት ለመስጠት ሁሉ ነገር የተመቻቸላቸው መስሎዋቸው ነበር፡፡ እንደጠበቁትና እንደተመኙት ግን አልሆን አለና ሥራ ሳያገኙ ለብዙ ጊዜያት ተንከራተቱ፡፡ እ.ኤ.አ በየካቲት 1771 መጨረሻ ላይ ራዲሼቭና ጓደኞቹ ኪቲዞቭና ኤ.ኬ. ሩቫኖቭስኪ

በሩሲያ ፓርላማ ውስጥ የፕሮቶኮል ሹም አማካሪነት ሥራ አግኝተው ተቀጠሩ፡፡ “የፕሮቶኮል ሹም አማካሪ” ተብሎ ለራዲሼቭ የተሰጠው ማዕረግ በፍጹም አላስደሰተውም፡፡ ይህንን ቅሬታውን ከጊዜ በኋላ “የኤፍ.ቪ ኡሻኮቭ አኗኗር” በሚለው መጽሐፉ ላይ አስፍሮታል፡፡ ቅሬታው የእርሱ ብቻ ሳይሆን ለመንግስት ቅርበት ያላቸውና የሩሲያን ለውጥና ዕድገት የሚናፍቁና የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚታገሉ ሌሎች ወጣቶች ጭምር ነበር፡፡ የሥነ-ጽሑፍ ተመራማሪዎች እንዳመለከቱት፤ ራዲሼቭ በፓርላማ /ዱማ/ ውስጥ መሥራቱ ብዙ ነገሮችን እንዲገነዘብ ረድቶታል፡፡ በፓርላማው ውስጥ ግፈኞችን ባለርስቶችን፣ አልጠግብ ባይ ባለስልጣኖች፣ ጉቦኞችንና ጉቦ አቀባዮችን፣ ሸፍጠኞችንና ፍትሕ የተነፈገውን የሩሲያ ህዝብ በሚገባ ለማወቅ ዕድል አግኝቶዋል፡፡ ራዲሼቭ ይህንኑ የዘራፊዎችንና የወሮበሎችን ዓለም ከአጤነ በኋላ ነው “የኤፍ - ቪ ኡሻኮቭ አኗኗር” የሚለውን ታሪክ የጻፈው፡፡ በዚህ ሥላቃዊ /Satirical/ ፅሑፍ ለሩሲያ ህዝብ ፍትህና ርትዕ እንደተነፈገው፣ ባለሥልጣኖቹ፣ ውሸት፣ ሸፍጥ፣ ሌብነትና አጭበርባሪነት የየዕለት ተግባራቸው እንደሆነ አትቷል፡፡ በሥነ ጽሑፍ ረገድ ታላቅ ችሎታ ከነበረው ግሪባየዶቭ ጋርም ስለአደረገው ትውውቅ ጽፏል፡፡
እ.ኤ.አ በጥር ወር 1772 ራዲሼቭ የተጠራቀመ የዓመት ፈቃዱን ወሰደና ወደ አባቱ ሀገር ሄደ፡፡ በዕረፍት ላይ በቆየበት ጊዜ የገባሮችን እውነተኛ ሕይወት በዐይኑ ለማየት ቻለ፡፡ ይህንንም “የሩሲያ ገባሮችን የኑሮ ሁኔታ ከዶክሜንት ሳይሆን በተጨባጩ በዐይኔ ተመልክቼ አረጋግጫለሁ” ብሏል፡፡ እ.ኤ.አ በ1773 በወቅቱ የሩሲያ ግዛት ወደ ነበረችው ፊንላንድ ሄደና ጄኔራል ያ.ኤን ብሩስ በሚመራው ክፍለጦር ውስጥ የመኮንኖች ፍርድ ቤት ይባል በነበረው መሥሪያ ቤት ዳኛ ሆኖ መሥራት ጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ በመጋቢት ወር 1775 በገዛ ፈቃዱ ራዲሼቭ ስራውን ለቀቀ፡፡ በመኮንኖች ፍርድ ዳኛ ሆኖ በሰራባቸው ዓመታት ከጓደኞቹ፣ ከወዳጆቹና ከቤተሰቦቹ በጣም ርቆ ስለነበር ደስታ አልተሰማውም፡፡ ከዚህም ተነሳ ወደ ናፈቃት ከተማ ወደ ፔ ተርቡርግ ተመለሰ። እንደተመለሰም ሊፒስጌ ዩኒቨርሲቲ እያለ ከተዋወቃት ወጣት አና ቫ ሊ የቭና ጋር ጋብቻ መሥርቶ መኖረ ጀመረ። በኋላ ዘመን ላይ ልጁ ኒኮላስ ራዲሼቭ ስለአባቱ ታሪክ በጻፈው ጽሑፍ ላይ ሲተነትን፤ “አባቴ
በአለቆቹ ዘንድ የተወደደና የተከበረም ነበር፡፡ ከፔተርቡርግ ማኅበረሰብ አባላት ውስጥ የተሻለ ሰው
ተደርጎም ይታይ ነበር፡፡ ለዚህ የአበቃው ደግሞ መማሩና አስተዋይም መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን በጭካኔ፣ በደምና በኹከት ላይ የተመሰረተው የፊንላንድ የመኮንኖች /የጦር/ ፍርድ ቤት ሥራ ላይ የሚያስተውለው ከቁጥጥር ውጭ የሆነው የመኮንኖች ድርጊት ለአባቴ አስደሳች አልነበረም” ብሏል፡፡ የራዲሼቭ ልጅ ኒኮላስ እንደጻፈው፤ በዘመኑ ግፍና ጭካኔ ተመላበት ሥራ መስራት በሩሲያ ውስጥ የተለመደ ነበር፡፡ በኢሜሊያ ፑጋቾቭ የገባሮች ዓመፅ የተቀሰቀሰውም ከዚሁ የተነሳ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1779 ራዲሼቭ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ፡፡ የኮሌጁ ፕሬዚዳንት ክቡር ጉታ/ግራፍ/ ኢ.ፒ ቮሮንትሶቭ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1780 በቮሮንትሶቭ መልካም ፈቃድ ራዲሼቭ የፔተርቡርግ ገቢና የፋይናንስ ቢሮ አማካሪ ሆኖ ተሾመ፡፡ በሥራው ጠንካራና ታማኝ፣ ኃይለኛም የነበረው ራዲሼቭ ፕሬዚዳንቱን ተክቶ በንግድ ሥራ ኮሌጅ ውስጥ የነበሩና የተከማቹ ችግሮችን እያቃለለ፣ አዳዲስ የአሰራር ስልት መቀየስ ሲጀምር ገንዘብ ሰብሳቢዎች ገንዘብ በማጉደልና ጉቦ
በመብላት አስቸገሩት፡፡ የውጭ አገር ሸቀጥም በኮንትሮባንድ መልክ እያስገቡ ይፈታተኑት ጀመር፡፡
ያቆጠቆው ሙስና /Corruption/ በእርሱ ጥረት ብቻ ሊጠፋ አልቻለም፡፡ ይህ ሁሉ የሥራ መደራረብና ኃላፊነትም እያለበት ራዲሼቭ በሥነ ጽሑፍ ረገድ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ ታላላቅ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ራዲሼቭ ከጻፋቸው መጻሕፍት ውስጥ የመጀመሪያው “የአንድ ሳምንት ማስታወሻ” የሚለው
ይገኝበታል፡፡ ይህ በሩሲያ የሴንቲሜንታል ሥነጽሑፍ ታሪክ ቀዳሚና የክላሲዝም መደምደሚያ ተደርጎ ታያል። ጊ.ኤ.ጉ ጎቭስኪ የተባለ የሥነጽሑፍ ሰው የራዲሼቭን ሥራዎች በጥልቀት አይቶ “ክፍለዘመኑ የሰው ልጅ ነፃነት፣ ግለሰባዊነት ፍላጎት፣ ሰብአዊ አኗኗር፣ ፍትሕ፣ የእኔነቱ ስሜ፣ ሥነ ልቡናው፣ የስሜቱ ነጸብራቅ የሆነው ባህሉና የፍልስፍናው ማስከበሪያ እንዲሆን ብሥራት ያበሥራሉ። የድሆቹ አስተሳሰብ ተቀባይነት እንዲኖረው ጦርነት ይከፍታሉ፡፡ የገባሩን ሥርዓት ይቃወማሉ” ብሏል፡፡   ራዲሼቭ “የአንድ ሳምንት ማስታወሻ” ብሎ የጻፈው መጽሐፍ የአንደ ሰው የዐሥራ አንድ ቀን
የብቸኝነት አኗኗር ነው፡፡ ከጓደኞቹና በአጠቃላይም ከሰው ልጅ ዕይታ ርቆ የጻፈው ይህ መጽሐፍ፤ ሰው ያለ ሰው ደስታ፣ ያለ ጓደኛ ፍቅር፣ ያለፍቅር ሕይወት ዋጋቢስ መሆኑን ያስረዳል። ራዲሼቭ “የአንድ ሳምንት ማስታወሻ”ን ከጻፈ በኋላ “ከፔተርቡርግ እስከ ሞስኮ የተደረገ ጉዞ” (ፑቲሼትቪየ

ኢዝ ፔተርቡርጋ ቨመስክቡ) የሚል ትልቅ መጽሐፍ ጽፎ አሳትሟል፡፡ በዚህ ድርሰቱ ስለ ግሪክ ፍልስፍና ያተተ ቢሆንም ትኩረት ያደረገው ግን በባላባትነታቸው በሚመጻደቁት በፔተርቡርግና በሞስኮ መሳፍንት ላይ ነው፡፡ ራዲሼቭ በዚህ መጽሐፉ ሲናገር፤“የገባር ሥሪት የብዙኃኑን አኗኗር ክዶ ለአናሳዎች የሚታገል መንግስታዊ ሥልጣንና ሀብት እንዲሁም ጉልበት የአለው የህዝቡን መብትም ሆነ ጥቅም እየገፈፈ ለራሱ የሚያደርግ፣ እንደልቡ የሚፈርድ፣ ለራሱ ህልውና የሚጨነቅ አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ የሆነ ሰው ሰራሽ መሳሪያ ነው” ብሎዋል፡፡ ራዲሼቭ ያልተገደበ ሥልጣን ለዛር መንግሥት አንሰጥም፡፡ ለዛራዊው መንግሥት ብቻ በሚስማማ ሕግ የምንመራ ከሆነ ሕዝቡ ኃላፊነቱን አይወጣም፡፡ ምርት አያመርትም፡፡ አይፈላሰፍም፡፡ ሩሲያ አታድግም፡፡ አሁን በአለንበት ነባራዊ ሁኔታ መንግሥት የሀገሪቱ የመጀመሪያ ዜጋ ሲሆን ሌሎቻችን

ዜግነት መብት የለንም፡፡” በማለት “ከፔተርቡርግ እስከ ሞስኮ የተደረገ ጉዞ” በሚለው መጽሐፉ ትንታኔ ሰጥቷል፡፡ ይህ መጽሐፍ የሩሲያን ሕዝብ ሕይወት ያካተተ ወጥ መረጃ /ዶክሜንት/ ተደርጎ ይታያል፡፡
መጽሐፉ በቀጥታ የተጻፈው በታላቋ ንግሥት በዳግማዊት ካቴሪና ዙሪያ በነበሩት የመንግሥት ባለሥልጣኖች ላይ ነው፡፡ ንግሥቲቱ በሩሲያ አዲስ የህገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ1766፣ አቋቁማ ጥገናዊ ለውጥ ለማድረግ የተነሳሳችው በዚሁ በራዲሼቭ መጽሐፍ ተደናግጣ ነበር፡፡ ራዲሼቭ በዚህ መጽሐፉ በሰነዘረው አስተያየት፤ “ሕዝቡ በደል ሲደርስበት በየትኛው ሕግ ባለሥልጣናቱንና በዳዮቹን ይጠይቃል? ሲል ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በመቀጠል “አሳሳቢው ጉዳይ” በሚል በጻፈው ሐተታ ሕዝቡ ለሕዛባዊ አብዮት እንዲነሣሣና የገባርነት ሥርዓት እንዲያከትም አሳሰበ፡፡ ይህ ጽሑፍ በምሥጢር ጭምር እየተባዛ ለህዝቡ ተዳረሰ። በተለይም የአሜሪካ ህዝብ እ.ኤ.አ ከ1776-1783 ለነጻነት የከፈለውን መስዋዕትነት እየጠቀሰ አርአያነቱን መከተል እንደሚገባ አስገነዘበ፡፡ ራዲሼቭን ለትግል ያነሳሳው ሌላው አብዮታዊ አስተሳሰብ ፑቫቾቭ መራው የገበሬ ዐመፅ ነው። “አሳሳቢው ጉዳይ” የሚለውን ቃል አስቀድሞ ሳይንቲስቱና ገጣሚው ሎሞናሶቭ ተጠቅሞበታል፡፡ ታላቁ ገጣሚ ዴርዣቪንም በዚህ ርዕስ ተጠቅሞ ሕዝቡን ለዓመጽ አነሣስቶበታል፡፡ በአሳሳቢው ጉዳይ /ቮልነስት/ የሕዝቡን አስተያየትና አስተሳሰብ ፈለግ አድርጎ ራዲሼቭ የቅስቀሳ ጽሑፍ
እያሳተመ ያሰራጭ ጀመረ፡፡ ገጣሚው በ“ቮልነት” በርካታ ግጥሞችን አሳትሞ አሰራጭቷል፡፡

ከግጥሞቹ ውስጥ የሚከተሉት ስንኞች ቀርበዋል፡፡
“ጠንካራው ወንድሜ ይኑርህ ድፍረቱ፣
የሀብት ምንጭ ነህ ታላቅ ነህ ከንቱ፡፡
መተኪያ የለህም አይኖርህም መቅኖ፣
አሳሳቢው ጉዳይ ፊትህ ተደቅኖ፡፡
ከአሥራት ተፈታ ይብቃህ ባርነቱ፣
አሳሳቢው ጉዳይ የኸው ነው በእውነቱ፡፡”
ይህ ግጥም በዘመኑ ለሩሲያ ሕዝብ ታላቅ ጥሪ ሆኖ - ቀረበ፡፡ ሌሎች ዘመናዊና ወቅታዊ ግጥሞችንም

እያፈለቀ ያሰራጭ ጀመር፡፡ ለዚህም “ተነሡ” የሚለው ግጥም ለአብነት ይጠቀሳል፡፡
“ተነሡ እንታገል ጓዶች ለነጻነት፣
መቆሙን አውቀናል ዘውዱ ለባርነት፡፡
ባላባት ባለርስት ጠግቦ ተንደላቅቆ፣
በማይገሰሰው በሥልጣኑ ደፍቆ፣
ከእንግዲህ አይኖርም ሕዝቡን አስጨንቆ፡፡
ጓዶች ሰምታችኋል የሩሲያን ዛር?
መለኮታዊ ነኝ ብሎ ሲናገር፣
ሥልጣን እንደሚያመልክ ይህ ነው ምሥክር፡፡
በጣም የተዋበ ጽጌረዳ አበባ ዛሩ እየቀጠፈ፣
ድህነት ብቻ ነው ለእኛ ያተረፈ፡፡”

Published in ጥበብ

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር፡፡
የኢትዮጵያውያን አባባል
ብዙ እጆች ሥራን ያቀላሉ፡፡
የታንዛንያውያን አባባል
ሁለት ጉንዳኖች አንድ አንበጣን ለመጐተት አያንሱም
የታንዛንያውያን አባባል
አንድ አምባር ለብቻው አይንሿሿም፡፡
የኮንጐአውያን አባባል
አንድ እንጨት ይጨሳል እንጂ አይነድም፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
በፍጥነት ለመጓዝ ከፈለግህ ብቻህን ሂድ፤ ሩቅ ለመጓዝ ከፈለግህ በህብረት ሂድ፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
ቤተሰብ እንደዛፍ ነው፤ ይጐብጣል እንጂ አይሰበርም
የዩቴ አባባል
የቅርብ ወዳጅ የቅርብ ጠላት ይሆናል፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
ጓደኛ ማጣት ከመደህየት እኩል ነው፡፡
የታንዛንያውያን አባባል
ለከብቶችም እንኳን ወጣትነት ውበት ነው።
የግብፃውያን አባባል
ቁንጅና ተሸጦ አይበላም፡፡
የናይጄሪያውያን አባባል
ቡናና ፍቅር የሚጣፍጠው በትኩሱ ነው፡፡
የኢትዮጵያውያን አባባል
ፍቅር ባለበት ጨለማ የለም፡፡
የቡሩንዲያውያን አባባል
ከአንተ የሚበልጥ እግር ያላት ሴት አታግባ።
የሞዛምቢካውያን አባባል
ትዕግስት ሁሉንም ችግሮች የሚፈታ ቁልፍ ነው፡፡
የሱዳናውያን አባባል
ስለሮጡ ብቻ ይደረሳል ማለት አይደለም፡፡
የስዋሂሊ አባባል
ትዕግስት ድንጋይ ያበስላል፡፡
የአፍሪካውያን አባባል

Published in ጥበብ

ኤርትራ በፕሬስ ነፃነት 180ኛ ወጥታለች (ከ180 አገራት)
ኢትዮጵያ ደግሞ ከ180 አገራት 142ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች

    የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ባለፈው እሁድ ሜይ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በመላው ዓለም ታስቦ ውሏል፡፡ (እኛ አገር ደግሞ በመወቃቀስ!) አሳዛኙ ነገር ግን ምን መሰላችሁ? ያለፈው 2014 ዓ.ም ለዓለም የፕሬስ ነፃነት እንቅፋቶች የበዙበት ዓመት ነበር፡፡ በመላው ዓለም በመረጃ ነፃነት ረገድ ከፍተኛ ማሽቆልቆል መታየቱን “ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ” የተሰኘው የሚዲያ መብት ተሟጋች ቡድን ገልጿል፡፡
እናላችሁ … ቡድኑ ባወጣው ሪፖርት፤ ባለፈው አንድ ዓመት በመላው ዓለም 25 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን 158 ጋዜጠኞች ታስረዋል፡፡ መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው ሌላው የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ቡድን (CPJ) በበኩሉ፤ ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያን በ2ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል - 17 ጋዜጠኞችን አስራለች በሚል፡፡
በነገራችን ላይ ጋዜጠኞችን በማሰርና የህትመት ሚዲያም ሆነ ኢንተርኔትን በማፈን ከዓለም ቁጥር 1 የተባለችው ጎረቤታችን ኤርትራ ናት፡፡ (ሌላው ቢቀር ምናለ ከእሷ እንኳ ራቅ ብንል?!)  ጋዜጠኞች የመንግስት ክስና እስር በመፍራት ለስደት የተዳረጉባት አገር በሚልም ጦቢያ ተነቅፋለች፡፡ በ2014 ዓ.ም 30 ጋዜጠኞች ለስደት ተዳርገዋል ይላል - ሪፖርቱ፡፡  (መንግሥት አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም ቢልም መብቱ ነው!)
ባለፈው እሁድ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት አስተባባሪነት (ካልሆነ እታረማለሁ!) በተከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ የግል መፅሄቶች በእያንዳንዱ ዕትማቸው ሊያስከስስ የሚችልና ህዝብን ለአመፅ የሚቀሰቅስ ነገር ይፅፉ የነበረ ቢሆንም መንግስት በ“ሆደ ሰፊነት” ችሏቸው መቆየቱን ገልፀዋል። (በጅምላ የተዘጉትን መፅሄቶች ለማለት ነው፡፡) እኔ በበኩሌ መንግስት “ሆደ ሰፊ” አልሆነም የሚል ክርክር የለኝም (“ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” አሉ!) የእኔ ጥያቄ ግን የመንግሥት “ሆደ ሰፊነት” ምን ፈየደ? የሚል ነው። ከምሬ እኮ ነው … ሆደ ሰፊነቱ ምን በጎ ነገር አመጣ? ይሄን ያህል መስዋዕትነት የተከፈለውስ ምን ለማትረፍ ነበር? ሁላችንም እንዳየነው ሁሉም የማታ ማታ ተከሰው፣ የሚዲያ ተቋማቱም ተዘግተው፣ አሳታሚዎችና ጋዜጠኞች ለስደት ነው የተዳረጉት፡፡ እናም መንግስት “ሆደ ሰፊነቱን” በአግባቡ የተጠቀመበት አልመሰለኝም (Abuse ነው ያደረገው!)
“ሆደ ሰፊነቱ” በዘመቻ ጠራርጎ ለመዝጋት ወይም ለመክሰስ ከሆነ ከዚህ እርምጃ አገርና ህዝብ እንዲሁም የግል ፕሬሱ ምን ተጠቀመ? እንኳን ሌላው ራሱ ኢህአዴግ መራሹ መንግስትም እኮ የተጠቀመው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ (ለጊዜው እፎይ ብሎ ይሆናል እንጂ!)
እኔ የምለው … ከጦቢያ ወፈ ሰማይ ስደተኞች መካከል ስንቱ በድህነት፣ ስንቱ በፖለቲካ፣ ስንቱ በባዕድ አገር ናፋቂነት፣ … ወዘተ ለስደት እንደተዳረገ መረጃ ቢደራጅ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ (ለመንግስት ተመቹም አልተመቹም እኮ ኢትዮጵያዊነታቸው አይፋቅም!!) በዚህ አጋጣሚ ለልማታዊ መንግስታችን የምመክረው ነገር ቢኖር (ደህና መካሪ ገጥሞት አያወቅማ!) ሁሉን “ጠላት” ከማድረግ እንዲቆጠብ ነው፡፡ (ከበቂ በላይ ጠላት እኮ ነው ያለን!)
እኔ እንደውም …. መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር ከድህነት ውጭ ጠላት ባይኖረው እመርጣለሁ፡፡ (ማን መራጭ አደረገህ እንዳትሉኝ!?!) እንዴ መንግሥት እንዴት ሳር ቅጠሉን ጠላት ያደርጋል?! አንዳንዴ ሳስበው አበሻ “ምቀኛ አታሳጣኝ” እንደሚለው ሁሉ ኢህአዴግም “ጠላት አታሳጣኝ!” የሚል ይመስለኛል፡፡ (ጠብ ጫሪ ሆኖ እኮ አይደለም!) በቃ ጠላት ሲኖር ብርታት ይሆነኛል ከሚል ባህላዊ አስተሳሰብ! ነው (ግን እኮ ጎጂ ነው!) ለነገሩ ተቃዋሚዎችም እኮ ያው ናቸው! በሆነ ተዓምር ኢህአዴግ የባህርይ ለውጥ ቢያመጣ እኮ ግራ ነው የሚገባቸው፡፡ ምክንያቱም ለእነሱ የፖለቲካ 101 ኢህአዴግን እስኪበቃው መስደብ ነው፡፡ (ይሄም ኋላቀርነት ነው!)
በነገራችን ላይ አቶ ሬድዋን ስለመፅሄቶቹ ያነሱት፣ እኔም በዛሬ ፅሁፌ የደገምኩት የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ሰበብ በማድረግ ስለሆነ ከነገር እንዳትቆጥሩብኝ። ደግሞም እኮ ውይይት አይከፋም፡፡ ማን ያውቃል አንደኛው ወገን እስካሁን ያልተየው ነገር ብልጭ ሊልለት ይችላል። ይታያችሁ … ኢህአዴግ አንድ ቀን (በቀኝ ጎኑ የተነሳ ዕለት መሆን አለበት!) ተነስቶ “በግል ፕሬሱ ጉዳይ እኔም ዘንድ ስህተቶች ነበሩ፤ ኢህአዴግ የመላዕክቶች ስብስብ አይደለም፤ አውቆ በድፍረት ሳያውቅ በስህተት ጥፋቶች ሊፈፅም ይችላል” ብሎ ቢናዘዝስ! (ማን ያውቃል አሉ!) ለጊዜው ግን ቅዠትና ህልማችንን ትተን ወደ ተጨባጩ እውነታ እንመለስ፡፡ እናላችሁ … ኢህአዴግ በመፅሄቶቹ ላይ አሳየሁት ያለውን “ሆደ ሰፊነት” አባክኖታል ባይ ነኝ፡፡ (“ሆደ ሰፊነት” መጥፎ ሆኖ እኮ አይደለም!)
ይሄውላችሁ … ለምሳሌ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ሂደት መጀመሪያ ላይ ደጋግሞ “ሆደ ሰፊነትን” ሲጠቅስ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከፓርቲዎች ጀርባ ላለው ህዝብና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ሲል እንደሆነ መግለፁ ትዝ ይለኛል፡፡ (አንዳንዶች መጨረሻው አላማረም ቢሉም!)
እናላችሁ … ኢህአዴግ/መንግስት ለግል መፅሄቶች አሳየሁት ያለው “ሆደ ሰፊነት” የግል ፕሬሱን ህልውና ለመታደግ ቢሆን ኖሮ ዋጋውን ከፍ ያደርግለት ነበር። “ለግሉ ፕሬስ ማበብ በፅናት የታገለ ፓርቲ!” ተብሎም ሲወደስ በኖረ! (አሁንም የሚያወድሱት አይኖሩም አልወጣኝም!)
በእርግጥ ይሄ ያለልፋት አይገኝም፡፡ ግን አሁን ከደረሰው ኪሳራ አይብስም፡፡ ከግል ህትመቶቹ አሳታሚዎችና አዘጋጆች ጋር በልበ ቀናነት ቢወያይና ቢመካከር እርግጠኛ ነኝ ለውጥ ይመጣ ነበር፡፡ (ከኢቲቪ ዶክመንተሪ ውይይት ይሻል ነበር!)፡፡ እንዳለ መታደል ሆነና ግን ሆደ ሰፊነቱን ከንቱ ያደረገ ውጤት ተከሰተ፡፡ በአንድ ጊዜ 6 መፅሄቶችና ሁለት ጋዜጦች ተከረቸሙ። የሚብሰው ደግሞ 30 የሚደርሱ ጋዜጠኞች ለስደት መዳረጋቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ተሟጋቾች ሪፖርት መነሻ ሆነናል፡፡ ከእነ ኤርትራና ሰሜን ኮርያ ጋር (አገራዊ ኪሳራ እኮ ነው!)
በእሁዱ የፕሬስ ነፃነት ቀን አንድ ጥናት አቅራቢ፤ CPJ የተባለው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ኤዲተር ላልሆኑ ሁሉ Best Editor of the Year እያለ ይሸልማል ሲሉ ወቅሰውታል፡፡ በነገራችን ላይ ይሄን ተቋም የሚተቹና የሚወቅሱ አብዛኞቹ ሰዎች “የተቋሙን ፕሬዚዳንት አውቀዋለሁ፤ ዳይሬክተሩ ወዳጄ ነው” ወዘተ … በማለት ነው የሚጀምሩት፡፡ (ነገሩን ማለቴ ነው!)
እኔ እንግዲህ CPJን በዝና እንጂ ብዙም አላውቀውም። ሽልማቱም … ስልጠናውም (ካለው ማለቴ ነው?!) አልደረሰኝም፡፡ ግን ቢያንስ ይሸልማል ተብሏል፡፡ እናም ነገር በሆዴ በላሁ፡፡ ኢህአዴግ ወይም መንግስት ባለፉት ዓመታት ስንቱን ጋዜጣና መፅሄት እንደዘጋ አስቡት - በ97 ምርጫ ማግስትና በተለያዩ ጊዜያት፡፡ ስንቱ የግል ፕሬስ ጋዜጠኛ እንደታሰረ፣ እንደተሰደደ አስቡት፡፡ ስንት ወቀሳና ውግዘት በኢቢሲ እንደወረደበትም አስቡት - የግሉ ፕሬስ!! ግን በ25 ዓመት የኢህአዴግ የስልጣን ዘመን አንድ የግል ጋዜጣ ወይም ጋዜጠኛ … ኤዲተር … ካርቱኒስት … ፎቶግራፈር እውቅና ወይም ሽልማት ሲሰጠው አላየንም አልሰማንም፡፡ (ማመልከቻ ከመሰለብኝም ይምሰልብኝ!)
አሁን ያልኳት ነገር የመንግስት ወይም ኢህአዴግ ሥራ ነው አልወጣኝም፡፡ ጋዜጦችንና ጋዜጠኞችን የሚሸልሙና የሚያነቃቁ የግል ተቋማት ግን የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ (የፕሬስ ካውንስል መቅደም እንዳለበት አልጠፋኝም!) ሆኖም ባለቤቶቹ ለየቅል ናቸው ብዬ ነው፡፡
እንግዲህ በዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሰበብ የጀመርኩትን የዓለም ፕሬስ መረጃዎች ጥቂት ላስቃኛችሁና ወጌን ልቋጭ፡፡ በነገራችን ላይ CPJ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ 10 በሳንሱር የታነቁ አገራትን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡ (ከቻይናም እንብሳለን እንዴ?) እናላችሁ … 1ኛ ኤርትራ፣ 2ኛ - ሰሜን ኮሪያ፣ 3ኛ ሳኡዲ አረቢያ፣ 4ኛ - ኢትዮጵያ፣ 5ኛ አዘርባጃን፣ 6ኛ - ቬትናም፣ 7ኛ - ኢራን፣ 8ኛ - ቻይና፣ 9ኛ ምያንማር፣ 10ኛ ኩባ …. ናቸው ተብለዋል፡፡ ሪፖርቱ ላይ እንደተገለፀው መንግስታት ሳንሱርን በተለያዩ መንገዶች ሊፈፅሙት ይችላሉ፡፡ አፋኝ የፕሬስ ህግ በማውጣት፣ ጋዜጠኞች ራሳቸውን ሳንሱር የሚያደርጉበት (Self Censorship የሚባለው ነው!) ስጋት በመፍጠር፣ ከአገር በማሰደድ ወዘተ እንደ CPJ ሪፖርት!በነገራችን ላይ በዚህ የCPJ ሪፖርት ውስጥ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም የተገመገመችው (የኒዮሊበራሎች አሻጥር አይደለም ማለት ነው!) እናም በመላው ዓለም 180 አገራት በጥናቱ ወይም በግምገማው ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ኤርትራ ከ180ኛ አገሮች 180ኛ ወጥታለች፡፡ (በፕሬስ ነፃነት ከዓለም ውራ ናት!) እኛስ? ጦቢያ 142ኛ ደረጃ ላይ ናት ተብሏል፡፡ በፕሬስ ነፃነት ላለፉት 5 ዓመት በተከታታይ 1ኛ የወጣችው ፊንላንድ ናት፡፡ ቀናሁባት! (በናታችሁ ቅኑባት!)
ከመለያየታችን በፊት ከኢንተርኔት ያገኘሁትን ቀልድ ልንገራችሁ፡፡ ሶቭየት ህብረት ከመበታተኗ በፊት ነው አሉ፡፡ የአሜሪካ ውሻ፣ የፖላንድ ውሻና የሶቭየት ህብረት ውሻ በአንድ ላይ ተቀምው ያወጋሉ፡፡
የአሜሪካው ውሻ፡- “በእኔ አገር ብዙ ከጮህክ ይሰሙህና ጥቂት ስጋ ይሰጡሃል”
የፖላንድ ውሻ፡- “ሥጋ ምንድን ነው?”
የሶቭየቱ ውሻ፡- “መጮህ ምንድን ነው?”
(በሶቭየት ህብረት የመናገር ነፃነት አለመኖሩን ለመጠቆም የተቀለደ ነው!)

Sunday, 10 May 2015 15:38

የነፃነት ጥግ

ነፃነት፤ ሰዎች መስማት የማይፈልጉትን የመናገር መብት ነው፡፡
ጆርጅ ኦርዌል
ሃላፊነት ለነፃነት የሚከፈል ዋጋ ነው፡፡
ኢልበርት ሁባርድ
መንግስት ገደብ ካልተበጀለት በቀር ሰው ነፃ አይሆንም፡፡
ሮናልድ ሬገን
ነፃነት የነፍሳችን ኦክሲጅን ነው፡፡
ሞሼ ዳያን
በመናገር ነፃነት አምናለሁ፤ ነገር ግን በመናገር ነፃነትም ላይ ሃሳባችንን የመግለጽ መብት ሊኖረን ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
ስቶክዌል ዴይ
ነፃነት ካልተጠቀሙበት የሚከስም ነገር ነው፡፡
ሃንተር ኤስ.ቶምፕሰን
የመፃፍና የመናገር ነፃነት ሰዎችን የማብሸቅ ነፃነትን ይጨምራል፡፡
ብራድ ቶር

ያ ሁሉ ግፍ ለምን?

   ከሠባ ሥምንት ዓመታት በፊት፤ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በቅዱሥ ሚካኤል በዕለተ ቀኑ ረፋድ ላይ የኢጣሊያዊቷን ልዕልት ልደት ምክንያት በማድረግ፤ የአዲስ አበባና የአካባቢው የፋሺስት ኢጣሊያ ገዢ ጄኔራል ግራዚያኒ፡- መኖሪያና መብል የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን ምንዱባን በቤተ መንግሥት ሠብሥቦ እየመገበ ሣለ ነው ድንገት በተከታታይ ሠባት ቦንቦች ወደ ጄኔራል ግራዚያኒ የተወረወሩት፡፡ ግራዚያኒ ጠረጴዛ ሥር ገባ፡፡ በአካባቢው ከባድ ድንጋጤ ሠፈነ፡፡ ለተወሰኑ ቅፅበቶች አካባቢው በጭሥ ታፈነ፡፡
ቦንቦቹን የወረወሩት፡- ይሄንን ግዳጅ ለመወጣት ለበርካታ ቀናት ምሥጢራዊ ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩት፤ በትውልድ ኤርትራዊ መሠረት ያላቸው በነፍሥና በመንፈሣቸው ልባቸው በኢትዮጵያዊነት የአገር ፍቅር የተሞላና የነደደ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን አብርሃም ደቦጭ እና ሞገሥ አሥገዶም ናቸው፡፡ አብርሃም ደቦጭና ሞገሥ አሥገዶም ቦንቦቹን ከወረወሩ በኋላ በፍጥነት ከአዲስ አበባ ከተማ በመውጣት ወደ ሠሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ማምለጣቸውን ጳውሎስ ኞኞ፡- “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” በተሰኘ መጽሐፉ ላይ ፅፎአል፡፡ በጣም የሚያሣዝነው፡- በመጨረሻ አብርሃም ደቦጭና ሞገሥ አሥገዶም ጐጃም ውስጥ መገደላቸውን ጳውሎስ ኞኞ በመፅሐፉ ላይ ጨምሮ ፅፎልናል፡፡
በእብሪት ያበጠውና በቦንብ ፍንጣሪ የቆሠለው ጄኔራል ግራዚያኒ፤ በቁጣ ነድዶ ለወታደሮቹ ኢትዮጵያዊ የሆነውን ሁሉ በጥይት ቁሉት አላቸው፡፡ “ፍጁት!...ያገኘኸውን ሁሉ ግደል!”
የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች፡- የጠመንጃ ቃታ የሣቡበት ጣታቸው እስኪዝል ድረስ በመላው አዲስ አበባ ዳር እስከ ዳር ተኩስ በመክፈት ያልታጠቀውን የከተማዋን ነዋሪ ህፃን ሽማግሌ፤ ነፍሰ ጡር አሮጊት ሣይሉ ኢትዮጵያዊ የሆነውን የአገሬውን ሰው ሁሉ በጅምላ በጥይት የቆሉት ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ጠመንጃ ያልታጠቁት የፋሺስት ወታደሮች በቆንጨራ፣ በገጀራ፣ በአካፋ፣ በመጥረቢያ ከፊታቸው ያዩትን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጭካኔ ጨፈጨፉት፡፡ በወቅቱ ብዙዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች የሣርና የገለባ (የምርቅ) ክፍክፋት ደረባ ጣሪያ ያላቸው ጐጆ ቤቶች በመሆናቸው ጣሊያኖች ከእልቂት ከፍጅቱ ሸሽቶ ወደቤቱ በሚገባው ኢትዮጵያዊ ላይ ሁሉ እሣት ለቀቁበት፡፡ በውስጣቸው የተሸሸጉ ኢትዮጵያውያን የሞሉባቸውን ጐጆ ቤቶች ሁሉ በእሣት አነደዷቸው፡፡ ከሚነድደው ጐጆ ውስጥ ወጥቶ ለማምለጥ የሚሞክረውን በጥይት ለቀሙት፡፡
አዲስ አበባ በነዋሪዎቿ ኢትዮጵያውያን የደም ጐርፍ ተጥለቀለቀች፡፡ በእሣት ላንቃ ተላፈች፡፡ በአዲስ አበባ ሠማይ ሥር ሞትና ጭስ ሠፈኑ፡፡ የሞት ጥላ በአዲስ አበባ አናት ላይ ተደፋ፡፡ ፍጅትና እልቂቱ፤ ጭፍጨፋና ቃጠሎው ረፋድ ላይ የጀመረ ሌሊቱን ሙሉ ዘለቀ። ጄኔራል ግራዚያኒ በተከፈተ መስኮት ለማየት የሚችለውንና የሚደረገውን የህዝብ የጅምላ ግድያና የኢትዮጵያዊ ትውልድ እልቂት እያየ ከት ብሎ ይስቃል፡፡
ለኢትዮጵያውያን በጣም አስጨናቂ የሆነው የሞት፣ የፍጅትና የእልቂት ጊዜ… ረዘመ እንጂ ከቶውንም ሊያጥር አልቻለም፡፡ ጅምላ ግድያውና ጭፍጨፋው ቃጠሎውና ሠቆቃው የካቲት አሥራ ሁለት የጀመረ ከሶስት እስከ አሥር ለሚደርሱ ተከታታይና ተጨማሪ ቀናት መቀጠሉን የታሪክ ተመራማሪና ተርጓሚ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ በተለያዩ ጥናታዊ መፃሕፍቱ ላይ ጽፎአል፡፡ እንዲሁም ሌሎች ገናና ኢትዮጵያውያን የታሪክ ተመራማሪዎች፤ እና ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ የውጪ አገር የታሪክ ምሁራን በተለያዩ መጽሐፎቻቸው ላይ በታሪክ ውስጥ የሞት ምዕራፍ፤ የሞት ፋይል ሊሠኝ የሚችለውን ይሄን ክንውን አሣምረው ጽፈውታል፡፡
ማናቸውም የበዛና የከበደ ሀዘን ልብን ይሠብራል፡፡ ነፃነት የሌለበት፤ ብሔራዊ ክብርና ልዕልና የተደፈረበት፤ ሠብአዊ ፀጋ ተፈጥሮአዊ ውበትና በጐነት የተዋረደበት፤ የበዛና የከበደ ሀዘን ደግሞ የበለጠ ይሠብራል ልንል ከምንችለው በላይ ብዙ ርቀት ይሄዳል፡፡
ሁሉም ባገር ነው፡- ሲሉ፤ በነፃነት ለማለት ነው፡፡ ሁሉም ነገር የሚያምረው በነፃነት ክብር በምትኖርባት የትውልድ አገርህ ላይ ነው ለማለት፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች ከሠላሣ ሺህ እስከ ሠማንያ ሺህ የሚደርሱ ያልታጠቁ ንፁህ ኢትዮጵያውያንን በግፍ በገፍ ፈጁ፤ ገደሉ፡፡ አዲስ አበባን በእሣት አቃጠሉ፤ አወደሙ፡፡ በወቅቱ በ1879 ዓ.ም መቆርቆር የጀመረችውና ከተመሠረተች ሃምሣ ዓመት የሆናት የአገራችን ርዕሠ መዲና አዲስ አበባ፤ በጅምላ እልቂትና ፍጅት በበረታ ከባድ የሀዘን መንፈስ ጣዕርና ጭንቅ በሞላበት የሞት ላንቃ በንፁሀን የደም ጐርፍና የደም ጩኸት ክፉኛ ተመታች። ሰሚ የሌለው ያልታጠቁ ንፁህ ኢትዮጵያውያን የደም ጩኸት ወይንም የንፁሀን የደም ጐርፍ ጩኸት!...
የጣሊያን ዜግነት የሌላቸው፤ የፋሺስት ኢጣሊያ የተለያዩ የቅኝ ግዛት አገር ወታደሮች፡- ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ካራባኔሪ ይባላሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ የቅኝ ግዛት አገር ኤርትራ ተወላጆች የሆኑ ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ካራባኔሪዎች አሉ፡፡ የጄኔራል ግራዚያኒ በቁጣ የነደደ ትዕዛዝ እንደተላለፈ፡- እነዚህ ባለጥቁር ሸሚዝ ካራባኔሪ የኤርትራ ተወላጆች፣ የጦር መሣሪያ ባልታጠቁ ንፁሀን ዜጐች ላይ አንተኩስም አሻፈረኝ በማለታቸው፤ የጣሊያን ዜግነት ባላቸው የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች እንዲረሸኑ ተደረገ፡፡ ትጥቃቸውን ፈትተው መደዳውን ሆነው በጠመንጃ አረር ተረሸኑ፡፡ በዚህ ውሣኔያቸው ጀግናም ሠማዕትም ናቸው። ባልታጠቁ ንፁሃን ሰዎች ላይ አንተኩስም በማለታቸው ጀግኖች ሲሆኑ፤ በዚህ ውሣኔያቸው ምክንያት በመረሸን በመገደላቸው ደግሞ ሠማዕት ናቸው፡፡
ይህ የፋሺስት ኢጣሊያ አረመኔነት የተመላበት አሠቃቂ የገፍና የግፍ ግድያና ጭፍጨፋ ኢትዮጵያውያንን ለከፋ ሀዘንና ለበዛ ሰብአዊና ቁሣዊ ጉዳት መዳረግ ብቻ ሣይሆን፤ የኢትዮጵያውያንን የኢትዮጵያዊነትና የፍትሀዊነት፣ የአገር ፍቅርና የነፃነት መንፈስ እጅጉን አስቆጣ፡፡ ዱር ቤቴ ላለው አርበኛም ሆነ በዱር በገደሉ ላልከተተው ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ ነፃነት የመጋደልና የመዋደቅ ብርቱ ጉልበት ሠጠ፡፡
አገራችንን በግፍ የወረሩ የፋሺስት ኢጣሊያ ኃይሎች ከእልቂትና ከፍጅት የተረፈውን ኢትዮጵያዊ ከአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሣይሆን ከመላው ኢትዮጵያ አካባቢዎች እያደኑ በተለያዩ እፍግፍግ ያሉ እሥር ቤቶች ውስጥ አጐሩት፡፡
ጥቂት ቆይተው ኢትዮጵያውያኑን ከተጨናነቁበትና ከተፋፈጉበት እሥር ቤቶች እያወጡ ወደ ኢጣሊያ አዚናራ፣ ወደ ቀይ ባህር ናኩራ ደሴቶች፣ ሶማሊያ ደናኔ የግዞት እሥር ቤቶች አጋዙዋቸው፡፡ ወደ ሶማሊያ ደናኔ እና ወደ ቀይ ባህር ናኩራ የግዞት እሥር ቤቶች የተጋዙት ኢትዮጵያውያን ግዞተኞች የተጫኑት በካሚዮኖች ሲሆን፤ በሚፈፀምባቸው ጭካኔ የተመላበት አስከፊ ግፍ ምክንያት በጉዞ ላይ እንዳሉ ህይወታቸው ያለፈው ጥቂት አይደሉም፡፡ በግዞት እሥር ቤቶቹም ሠውነታቸውን በምላጭ እስከመተልተል የሚደርስ ጭካኔ የተመላበት ኢሠብአዊ ድርጊትና ተፈጥሮአዊ ጥፋት ተፈጽሞባቸዋል።
*   *   *
ግን ለምን?  
ከሠባ ስምንት ዓመታት በፊት የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የጦር መሣሪያ ያልታጠቁ ንፁሀን ኢትዮጵያውያንን እንዲያ በገፍና በግፍ የፈጁ የጨፈጨፉት ለምንድነው? ይሄ ሁሉ ጭካኔና ግፍ ለምን አስፈለገ? ይሄ መጠነ ሠፊ የትውልድ እልቂት እንዲፈፀም በቁጣ የነደደ ትዕዛዝ ላስተላለፈው ጄኔራል ግራዚያኒ መታሠቢያ ሀውልት እንዲሠራ የሚል ሃሳብ የሚመነጨው እንደምን ካለ ህሊና ነው? እንደምን ካለ አእምሮ?
*   *   *
በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ ይህ እስከዚህ የተወሳው በገፍ የተፈፀመ ግፍ ግድያ፣ ፍጅትና እልቂት ከተከወነ ሰባ ስምንት ዓመታት አልፈዋል፡፡ ለአምስት ዓመታት በተደረገ ፀረ ፋሺስት ተጋድሎ በመጨረሻ ፋሺስት ኢጣሊያን እኛ አሸንፈን፤ ከመላው ኢትዮጵያ ምድረ ገጽ ረግጠንና ጠራርገን በማስወጣት ባለፈው ማክሰኞ ሠባ አራተኛ ዓመቱን የድል ቀኑን ባከበርነው ዕለት፤ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የድል ሠንደቃችን ከተጣለበት አንስተን፣ በክብር በማውለብለብ የኢትዮጵያን ድልና ነፃነት ለዓለም ሁሉ አውጀናል፡፡
ለጀግኖች አባቶቻችን፣ ለጀግኖች ወላጆቻችንና ለእኒያ ሠማዕታት ክብር ይሁን! የጀግኖች ሠማዕታትን የመስዋዕትነት ፍሬዎችንና የአባቶቻችን ርስት አንሰጥም፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
ሠላምዎ ይብዛ በፍቅር!
Soli Deo Gloria!

Published in ህብረተሰብ

 የሀገራችን ልዩ ልዩ ቅርሶችና የታሪክ ማስረጃዎች ዋሻ ውስጥ ጭምር መገኘታቸው እሙን ነው። ከዚህም ባሻገር ዋሻዎች የቤተክርስቲያን መልክ እንዲይዙ ተደርገውና ተፈልፍለው በመቅደስነት፣ በቅድስትነትና በቅኔ ማህሌትነት እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ርእሰ ጉዳይ መሠረት አድርጌ ላስነብባችሁ የፈለግሁትም የታላቁ ገዳም የዲማ ጊዮርጊስ ጽላተ ሕግ ስለሚኖርበት የተፈጥሮ ዋሻ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ሚያዚያ 23 ቀን በየዓመቱ የዓለም ወዝ አደሮች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበርበት ዕለት ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በአለበት ሁሉ ዓመታዊ የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጉስ በዓለ ንግሥ በምዕመናን ዘንድ ታስቦ እንደሚውል የታወቀ ነውና እኔም ወደ ታላቁ ገዳም ዲማ ጊዮርጊስ ብቅ ብዬ ነበር፡፡ ውቃቢ የሸሻቸው፣ ሰይጣን ያበላሻቸውና በእስልምና እምነት ሽፋን የሚንቀሳቀሱት እስማኤላውያንና አማሌቃውያን የአይኤስ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች በቅርቡ የንጹሐን ኢትዮጵያውያንን አንገት ቀልተው እንደፈጇቸው ሁሉ የቀድሞ የግብር አባታቸው የፋርሱ ንጉሥ ዱድያኖስም ነውርና ኃጢአት የሌለበትን የቅዱስ ጊዮርጊስን አንገት በሰይፍ ቀልቶ የገደለው በሚያዚያ ወር ላይ ስለሆነ ድርጊቱ የኢትዮጵያውያን ሰማዕታትን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያመሳስል ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የክብር አክሊል ይጠብቃቸዋል፡፡
የልዳው ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ከሚከበሩት ሰማዕታት አንዱ በመሆኑ ዘንድሮም ዲማ ውስጥ በዓለ ንግሡ ሲከበር ልዩ ድምቀት ነበረው፡፡ የዲማ ጊዮርጊስ ሥርዓተ ማህሌት ጥንታዊ ወጉንና ከብሩን የጠበቀ ነው፡፡ ወረቡ ድፋቱ፣ አብቸቦው፣ የከበሮ መረግዱና ዝማሜው ልብ ይመስጣል። በዋዜማው ላይ የሚወርደው ቅኔ ምሥጢር ያማልላል። ስለቤተክርስቲያኑ ውስጣዊ ውበት፣ በባህላዊ መንገድ ስለተሣሉት ሥዕላት፣ ወጥ ስለሆኑት ረጃጅም የእንጨት በሮች፣ መቃኖችና መስኮቶች፤ ስለነጋሪቶች፣ ከበሮዎች፣ እምቢልታዎች፣ በቅዳሴ ጊዜ ካህናትና ዲያቆናት ስለሚያደርጓቸው ወርቅና የብር አክሊሎች በቃላት ለመግለጽ ያዳግታል፡፡ የቀድሞ ነገሥታት ያበረከቷቸው ዘውዶች፣ የወርቅ ጫማዎች፣ ልዩ ልዩ አልባሳት በገዳሙ ይገኛሉ። የቀድሞው ንጉሥ ከነባለቤታቸው፣ ያበረከቱት የሥጋጃ ስዕልም በቅርስነት ተቀምጧል፡፡ የጻድቃንና ሰማዕታት ተጋድሎ በየሥዕላቱ ሥር በአጫጭር የግዕዝ ቋንቋ ተጽፎ ይታያል፡፡ እያንዳንዱ ሥዕል የራሱ የሆነ መግለጫ አለው፡፡ ጣራው ላይ ያለው የመላእክት ሥዕል ታይቶ አይጠገብም፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ ረጅም ጣሪያ ላይ መላእክቱ ተስለው ቁልቁል ሲመለከቷቸው በቅጽበት ወደ መሬት የሚወርዱ ይመስላሉ፡፡ ይህንኑ ያስተዋለ አንድ ደብር ወርቅ ደብተራ በመላእክቱ ሥዕል አዝኖ ዲማዎችን በራሳቸው ቅኔ ማህሌት ቆሞ በቅኔ እንዲህ ብሎ ሰደባቸው ይባላል፡-
“እም አይሁድ አይሁደ
እመ ይትሌዓሉ
“መላእክት በሰማይ ሰቀሉ፡፡ ዲሞች ከአይሁድ ይልቅ አይሁዶች ስለሆኑ መላእክትን በጠፈር ላይ ሰቀሉዋቸው። አይሁድ ግን ክርስቶስን የሰቀሉት በመሬት ላይ ነው፡፡” እንደማለት ነው፡፡  ገዳሙም የሴትና የወንድ ተብሎ በሚገባ የተደራጀ ነው። የንባብ ቤቱ፣ ዜማ ቤቱ፣ የቅኔና የሐዲሳት ማስመስከሪያ እንዲሁ በወግ በወጉ ተደራጅቷል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም ገዳሙ ዘመናዊ ሙዚየም ለመገንባት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ የገዳሙ መስራች ሾዔው አባ ተክለ አልፋ ናቸው፡፡ ክብረበዓላቸው ታህሳሥ 8 ይታሰባል፡፡
በገዳሙ ውስጥ የበርካታ ጻድቃንና ሰማዕታት ስሞች የተቀረጸባቸው ታቦታት ሲኖሩ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላተ ክብር ግን በአስገራሚው የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ መኖሩ አስደናቂ ነው፡፡
የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦተ ሕግ በዚያ አስፈሪና ግርማዊ በሆነ የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ ከመቼ አንስቶ መኖር እንደጀመረ ያስረዳኝ ባይኖርም ዋሻውን ከዲማ ጊዮርጊስ በስተግራ በኩል በግምት 1 ኪ.ሜ ከተጓዙ በኋላ ጸበሉ በአለበት የገደል አፋፍ ላይ ሆኖ ማየት ይቻላል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላተ ክብር የሚኖርበት ዋሻ በዲማና በግርኛ ማርያም ቤተክርስቲያናት መካከል በሁለተኛው የገደል እርከን ስር ይገኛል፡፡ ታቦቱ ከዋሻው ውስጥ ከመውጣቱ በፊት በእምብርክክ የሚያስኬደውን መንገድ ቁልቁል መውረድና ሽቅብ መውጣት ይጠይቃል። አባ ተከስተብርሃን የተባሉ አባት ታሪክም በገዳሙ ውስጥ በሰፊው ይተረካል። አባ ከሰተብርሃን በዲማ ጊዮርጊስ ገዳም የኖሩና የትሩፋት ሥራ ሰርተው ያለፉ የበቁ አባት ናቸው፡፡ እኒህ አባት ፆም በቀኖና በብህትውና በዋሻው ውስጥ ሲኖሩ ከትውልድ ቦታቸው አንዲት አህያ የሽንብራ ስንቃቸውን ጭና አድርሳላቸው ወደ አገሯ ትመለስ ነበር ይባላል፡፡ የትሩፋት ሥራ በመሥራት ላይ እንዳሉ ሥራቸውን ሳይጨርሱ፣ ፀሐይ ከምዕራብ የመግቢያ መስኮትዋ ላይ ደረሰች፡፡ በዚያ ወቅት “ሥራየን ሳልፈጽም አትጥለቂ” ብለው ሲገዝቷት ጨለማው ብርሃን በብርሃን ይሆናል፤ ከዚህም የተነሳ ነው ስማቸው አባ ተከስተ ብርሃን የተባለው፡፡
አባ ተከስተ በጾምና በቀኖና ላይ እንዳሉ በዋሻው ውስጥ ያርፋሉ፡፡ የዲማ ካህናትና መነኮሳትም ዋሻ ውስጥ በሕይወት ያሉ መስሎዋቸው ሲኖሩ በትራቸው ከዋሻ ተነሥታ ወደ ዲማ በመሄድ ሞታቸውን አስረድታለች፡፡ በትራቸውም በአሁኑ ሰዓት ዲማ ውስጥ አለች ይባላል፡፡
ዋሻው በእጅጉ የሚያስፈራ ሲሆን በዕለቱ በግርኛ ማርያምና በዲግ በኩል ባለው መግቢያ ሰው በገደሉ ላይ እየተንሸራተተ ወርዶ፣ ወደ ዋሻው አናት ላይ ሲወጣ ሲታይ በየገደሉ እየተንጠላጠለ ቅጠል የሚያሳድድ የፍየል መንጋ ይመስላል፡፡ ከዋሻው ጫፍ እስከ ጫፍ ለመድረስ ሁለት ጧፍ ይጨርሳል፡፡ ዋሻው ውስጥ ሲገባ ጧፍ እየተበራ ነው፡፡ ከዋሻ ውስጥ በጸበልነት የሚያገለግል ትልቅ ባሕር አለ፡፡ የጸበሉ መልክ ጥቁር ቡና ይመስላል፡፡
የጊዮርጊስ የንግሥ በዓል ሲቃረብ የበቁና ቅድስና ያላቸው አባቶች ወደ ዋሻ ውስጥ ይገቡና ለ7 ቀን እፍኝ ሽምብራ እየተመገቡ ሱባኤ ይገባሉ። ሲያስታኩቱና ቦታውንም ሲያጥኑ፣ ፈጣሪን ሲያመሰግኑ ይሰነብታሉ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲሆን ታቦቱ ለንግሥ ይወጣና በመጀመሪያ ከገደሉ እርከን ሥር በተተከለለት ድንኳን ይገባል፡፡ ከዚያም ወደ ሜዳ ታጅቦ ከወጣ በኋላ በእልልታ፣ በሆታ፣ በጭብጨባ፣ በከበሮ ድምጽ እየታጀበ ሄዶ ዲማ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ይገባል፡፡ በራሱ ጊዜም ተመልሶ ወደ ዋሻው ይገባል፡፡
የፍጡነ ረድኤቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ከመንበረ ክብሩ ሲወጣና ወደ መንበረ ክብሩ ሲመለስ በአውሎ ነፋስ ይታጀባል ይላሉ አባቶች። አንድ አባት እንዳወጉኝ፤ አንድ የበቁ ጻድቅ ታቦተ ሕጉን ከዋሻ ውስጥ ለማውጣት ጧፍ እያበሩ ወደ ዋሻው ሲገቡ፣ አንዲት የሌት ወፍ የሚበራውን ጧፍ በክንፍዋ መትታ ታጠፋባቸዋለች፡፡
ጻድቁ ተስፋ ሳይቆርጡ በዳበሳ ታቦተ ሕጉ ወደ አለበት ቦታ ደርሰው ታቦቱን በጨለማ ሲነኩት አምስቱም ጣቶቻቸው እንደጧፍ ያበራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ጽላቱ አንደበት አውጥቶ “አባ ተጠነቋቆልን” አላቸው ይባላል፡፡
ከዋሻው አቅጣጫ ከሜዳው ላይ ከገደሉ አፋፍ ደግሞ ሌላ ትንግርት አለ፡፡ አንድ ወቅት በዚያ አለታማ መንገድ አንዲት መነኩሴ ስትሄድ አንድ የጠገበ ጐረምሳ ክንዷን ይዞ ሊጥላት ሲል፤ “አቤት አቤት ፍጡነ ረድኤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድረስልኝ” ብላ ትጮሃለች፡፡ ወዲያው ፍጡነ ረድኤቱ ያንን አለት ሰንጥቆ ይደርስላትና ያንን ባለጌ ወጣት ቀሰፈው ይባላል፡፡ እናም አሁን ድረስ የፈረሱ ኮቴ፣ ጦሩ ያረፈበት ድንጋይ ይታያል፡፡ በደማሚት የማይፈርሰው ጥቁር አለትም እስከ ታች ድረስ ክፍት ሆኖ ሰው ይሾልክበታል፡፡  

Published in ህብረተሰብ

ታሪክ፤ ‹‹ህይወት እና እርምጃን›› መለስ ብሎ የማየት ጥበብ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ፤ ሚያዝያ 27 የተከበረውን ‹‹የኢትዮጵያ አርበኞች መታሰቢያ›› በዓልን ሰበብ በማድረግ፤ ከ73 ዓመታት በፊት፤ ሮበርት ጋሌ ውልበርት (Robert Gale Woolbert) የተባለ ፀሐፊ፤ በ‹‹ፎሪን ፖሊሲ›› መፅሔት፤ ‹‹የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ›› (The Future of Ethiopia) በሚል ርዕስ ባወጣው አንድ መጣጥፍ ያቀረበውን አስተያየት በመዳሰስ ታሪክን ለመዘከር ሞክሬያለሁ፡፡
ይኸው ፀሐፊ፤ ጁላይ 1936 ዓ.ም (እኤአ)፤ ‹‹The Rise and fall of Abyssinian Imperialism›› በሚል ርዕስ ያቀረበው ሌላ ፅሑፍ አለው፡፡ ኢትዮጵያ በጣሊያን ስትወረር ከፍ ሲል በተጠቀሰው ርዕስ ፅሁፍ ያቀረበው ይህ ፀሐፊ፤ ነፃነቷን ባገኘች ማግስትም ‹‹የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ›› (The Future of Ethiopia) በሚል ርዕስ ሌላ ፅሑፍ አስነብቧል፡፡ ውልበርት፤ ኢትዮጵያን እንደ ‹‹አፍሪካ በቀል›› ኢምፔሪያሊስት ኃይል ይገልፃታል፡፡ እናም ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ፤ ‹‹የአፄ ኃይለስላሴ መንግስት መፈራረስ፤ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የመጨረሻ ሐገር በቀል ኢምፔሪያሊስት የሆነ አንድ መንግስት ግብዓተ መሬቱ ተፈፀመ›› በማለት ፅፎ ነበር፡፡
ውልበርት፤ ‹‹የዓለም ኃያል መንግስታት የሰሜን - ምስራቅ አፍሪካን በቀጥታ ከመቆጣጠር ይልቅ፤ የቱርክ፣ የግብፅ እና የአቢሲኒያ ኤምፓየሮች እንዲስፋፉ በማድረግ የአውሮፓን ስልጣኔ በተዘዋዋሪ መንገድ ሥር እንዲይዝ ለማድረግ መሞከር ይበጃል›› የሚል አመለካከት እንደ ነበረ ጠቅሶ፤ ብዙ ሳይቆይ የቱርክ ኤምፓየር መፈራረሱን እና የግብፅ መንግስት ግዛት እያስፋፋ ኑቢያን፣ ኮርዶፋን እና ስናርን እንደተቆጣጠረ ይገልጻል፡፡
ግብፅ ከዚህም በላይ ግዛቷን ለማስፋፋት ትፈልግ ነበር የሚለው ይኸው ፀሐፊ፤ በወታደራዊ ኃይል የናይል ወንዝ ምንጭን ለመቆጣጠር በነበራት ፍላጎት የነጭ አባይን (ኋይት ናይል) መነሻ ለመቆጣጠር ችላ እንደ ነበር፤ እንዲሁም የአውሮፓ እና የአሜሪካ የጦር መኮንኖችን በጦርነቱ እንደተጠቀመች ይናገራል፡፡ ለምሣሌ፤ ከ1869 እስከ 1878 ዓ.ም (እኤአ) ባሉት ዓመታት አርባ ዘጠኝ የሚደርሱ በአሜሪካ ‹‹ሲቪል ዋር›› (የነፃነት ትግል) ተሳታፊ የሆኑ ጀነራሎችን በጦርነቱ አሰልፋ ነበር፡፡  
ግብፅ፤ የአሜሪካ እና የአውሮፓ የጦር መኮንኖችን ተጠቅማም፤ ኢትዮጵያን መያዝ አልቻለችም፡፡ በሂደትም እየተዳከመች መጣች፡፡ ኢስማይል የተባለው የግብፅ ንጉስ፤ ግዛቱን የማስፋፋት እና ስዊዝ ካናልን የመገንባት ትልቅ ምኞቱን ለማሳካት፤ ሐገሪቱን ለአራጣ አበዳሪ ሊሸጣት ተቃርቦ ነበር፡፡ በዚህ ተነሳ ችግር ውስጥ ገባ። በመጨረሻም ግብፅ በ1882 ዓ.ም (እኤአ) ከእንግሊዝ እጅ ወደቀች፡፡ ሱዳንም ከእጇ ወጣች፡፡ በቀይ ባህር ዳርቻ፤ ከምፅዋ በስተደቡብ የነበራት ግዛትም በጣሊያን ተወሰደ፡፡ በዚህም፤ በአፍሪካ ኤምፓየር የመመስረት ፍላጎትዋ እንደ ጉም በኖ ጠፋ፡፡
ኢትዮጵያ ለቅኝ ገዢዎች ሴራ ሳትንበረከክ ቆየች። ሮበርት ጋሌ ውልበርት  ‹‹ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ ለመኖር የቻለችው፤ በአስቸጋሪ መልክዐ ምድር የምትገኝ ሐገር በመሆኗ ነው›› ቢልም፤ ነገሩን በዚህ ብቻ ወስኖ ለማለፍ አልሞከረም፡፡ እንደ ውልበርት ሁሉ፤ ሌሎች የአውሮፓ ቅኝ ገዢ ፀሐፊዎች፤ ‹‹ኢትዮጵያ በተራራ የተከበበች ሐገር በመሆኗ የተነሳ በጦር ለመውጋት የማትመች ስለሆነች ቅኝ ገዢዎች ሊቆጣጠሯት አልቻሉም›› ብለው ለመደምደም አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ነገስታት የአመራር ብቃትን ለዓላማቸው አለመሳካት ምክንያት አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡ ውልበርት፤ አፄ ዮሐንስ፣ ምኒልክ እና ኃይለስላሴ ልዩ የመሪነት ብቃት በተፈጥሮ የታደሉ መሆናቸውን ገልፆ፤ በተለይ አፄ ምኒልክ ከሌሎቹ ላቅ ያሉ መሆናቸውን ያነሳል፡፡
በዚህ የተነሳ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች፤ ኢትዮጵያ የማትሞከር ሆናባቸው ተወት ሲያደርጓት ‹‹አልሰሜን ግባ በለው›› እንደሚባለው ሆኖ፤ አፍሪካን በመቀራመት ሂደት አርፍዳ የመጣችው ጣሊያን፤ በጉምዥት፣ ባለማመወቅ እና አማራጭ በማጣት ጭምር ኢትዮጵያን ለመያዝ ተመኘች፡፡ ሞከረች፡፡
በነፃነት ማግስት
ከፍ ሲል እንደገለጽኩት፤ በዚህ መጣጥፍ የማተኩረው፤ ሮበርት ጋሌ ውልበርት፤ ‹‹የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ›› (The Future of Ethiopia) በሚል ርዕስ ባቀረበው ፅሑፍ ላይ ነው፡፡ ፀሐፊው ይህን ጽሁፍ ባሳተመ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ ገና ነፃነት ማግኘቷ ነበር፡፡ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ገና ግልፅ አልነበረም። ስለዚህ ‹‹ኢትዮጵያ ከአክሲስ ፓወር ቁጥጥር ነፃ ብትወጣም፤ አሁንም ነፃነቷ ፈተና እንደተጋረጠበት ነው›› ይላል፤ የፎሪን ፖሊሲ መፅሔት ፀሐፊው ሮበርት ጋሌ ውልበርት:: ውልበርት፤ የዛሬ 73 ዓመት በኤፕሪል 1942 እትም ላይ ባቀረበው መጣጥፉ፤ ‹‹የአክሲስ ኃይሎች›› ከሚባሉት ሦስት ሐገራት፤ (ጣሊያን፣ ጀርመን እና ጃፓን) አንዷ በሆነችው ጣሊያን፤ ‹‹በመጀመሪያ የተወረረች ሐገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ነፃነትን በመቀዳጀትም የመጀመሪያዋ ሐገር ነበረች›› ይላል፡፡
ሌሎች ‹‹በአክሲስ ፓወር›› የተወረሩ ከደርዘን በላይ ሐገሮች ነበሩ፡፡ ታዲያ ይህን ‹‹የአክሲስ ኃይሎችን›› እንቅስቃሴ ለመግታት ህብረት የፈጠሩ ሦስት ሐገሮች (አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ሩሲያ) ነበሩ፡፡ እነሱም ‹‹አላይድ ፓወር›› በሚል ይጠቀሳሉ፡፡ እናም ‹‹በአክሲስ ኃይሎች›› ቁጥጥር ሥር የነበሩት ሐገሮች፤ በ‹‹አላይድ ፓወር›› ድጋፍ ነፃ ወጡ፡፡ በ‹‹አላይድ ፓወር›› ትብብር በመጀመሪያ ነፃ የወጣችው ሐገርም ኢትዮጵያ በመሆኗ፤ ‹‹አላይድ ፓወር›› ነፃ እንዲወጡ ያገዟቸውን ሐገራት ጉዳይ በተመለከተ ላራመዱት ፖሊሲ የመሠረት ድንጋይ የሆነ ሥራ የተሰራው የኢትዮጵያን ጉዳይ ከመፍታት ጋር ተያይዞ ነበር፡፡ ሆኖም እንደ መፅሔቱ ዘገባ፤ የጣሊያንን ኃይል በማንበርከክ ዘመቻ ወሳኝ ኃይል የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ነበር፡፡
‹‹አላይድ ፓወር››፤ ሐገራቱን መልሶ በመገንባት ሂደት ለተከተሉት አካሄድ እንደ ቀመር ሆኖ የሚያገለግል ፖሊሲ ሲነድፉ፤ የኢትዮጵያን ሁኔታ መሠረት አድርገው ነበር፡፡ ቀመሩን በመፍጠር ሂደትም ልዩ ጥንቃቄ አድርገዋል፡፡ ምክንያቱም፤ የ‹‹አላይድ ፓወር›› ፖሊሲ እና አሰራር በስደት በሚገኙ መንግስታት፤ እንዲሁም ‹‹በአክሲስ ፓወር›› ቁጥጥር ሥር ባሉ ሐገራት ህዝቦች እይታ ሥር መሆናቸውን ተረድተዋል፡፡ ይህን መረዳት ብቻ ሣይሆን፤ የተሳሳተ ሥራ በመሥራት ‹‹የአክሲስ ፓወር›› ሐገራት፤ ለፕሮፓጋንዳ የሚሆን ስንቅ እንዳያገኙ ሥጋት አድሮባቸው በጥንቃቄ መሄድን መርጠዋል፡፡    
በምሥራቅ አፍሪካ፤ የጣሊያን ፋሽስታዊ ኃይል የመጨረሻ የሽንፈት ፅዋውን የጨለጠው እኤአ ኖቬምበር 28፣ 1941 ዓ.ም ጎንደር ውስጥ በተካሄደ ጦርነት ነበር። በዚህ ጦርነት፤ የእንግሊዝ ኤምፓየር፤ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከምዕራብ አፍሪካ፣ ከሮዴሽያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን እና ከህንድ የተውጣጡ ወታደሮች በጦርነቱ እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡ እንዲሁም፤ የቤልጀም ቅኝ ከነበረችው ኮንጎ እና ነፃነት ከተቀዳጁ የፈረንሳይ የአፍሪካ ቅኝ ሐገራት የተውጣጡ ወታደሮችም ነበሩበት፡፡
የ‹‹አላይድ ፓወር›› ለኢትዮጵያ አርበኞች እገዛ አደረገ እንጂ፤ ዋና መመኪያ ኃይል የነበሩት፤ የኢትዮጵያ አርበኞች ናቸው፡፡ የ‹‹አላይድ ፓወር›› በመልሶ ግንባታ ሂደት ለተከተሉት ፖሊሲ አንድ መነሻ ሆኖ ያገለገለውም ጉዳይ ይኸው ነበር፡፡ ሌላው ጃንዋሪ 2፣ 1942 ዓ.ም (እኤአ) የተመድ አባል ሐገራት በአሜሪካ ዋሽንግተን ተፈራርረመው ያወጡት መግለጫ ነው፡፡
ይህን የጋራ መግለጫ መሠረት አድረገው ከኢትዮጵያ ጎን ከተሰለፉ ሐገራት በተጨማሪ፤ የፋሽስት ጣሊያን በሀገሪቱ ላይ የከፈተውን ጦርነት በመቃወም ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፉ፤ ፀረ ኢምፔሪያሊስት አቋም ያላቸው (ጥቁር አሜሪካውያን ጨምሮ) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ጥቁሮች  ነበሩ፡፡
ከዚህ ሌላ፤ አሜሪካ ‹‹ቃኘው ሻለቃ›› የተባለ ወታደራዊ ጣቢያ በኤርትራ በመገንባቷ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስባት ነበር፡፡ ‹‹ቃኘው ሻለቃ›› የተገነባው ለ‹‹አላይድ ኃይሎች›› የጦር መሣሪያ ለማቅረብ እና የጥገና አገልግሎት ለመስጠት ነበር፡፡ እንግሊዝ እንደገና በቆመው የአፄ ኃይለ ስላሴ መንግስት ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ለአሜሪካ ትርጉም የሚሰጣት ከዚህ የተነሳ ነው፡፡
ቤኒቶ ሙሶሎኒ ጁን 10፣ 1940 ዓ.ም (እኤአ) የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም፤ አዲስ ያቀናውን የምሥራቅ አፍሪካ ኤምፓየር ለአደጋ አጋልጦ ነበር፡፡ ዱቼ ሞሶሎኒ፤ በጊዜው የያዘው አንድ የተሳሳተ ስሌት ነበር፡፡ ሙሶሎኒ፤ ‹‹የፈረንሳይ ኃይል እየተዳከመ ሲመጣ፤ እንግሊዝም ወደ አዘቅት ትወርዳለች›› የሚል የተሳሳተ ግምት ነበረው። ይህም በሰሜን-ምሥራቅ አፍሪካ ሰፊ የጣሊያን ግዛት ለመመስረት የሚስችል አዲስ ዕድል እንዲከፈት ያደርጋል የሚል እምነት ነበረው፡፡ ሆኖም፤ ይህ ስሌት የተሳሳተ ነበር፡፡ የፋሽስት ጣሊያን መንግስት፤ የምሥራቅ አፍሪካ ግዛቱ ከጣሊያን የራቀ እና በቀላሉ ግንኙነት ለማድረግ የማያስችል በመሆኑ፤ ለማስተዳደር ማስቸገሩ አይቀርም።
የእንግሊዝ መንግስት በ1938 ዓ.ም (እኤአ) ኢትዮጵያ የጣሊያን ቅኝ ስለመሆኗ ዕውቅና ሰጥቶ ነበር። የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፤ አፄ ኃይለ ስላሴ በስደት ሎንዶን እንዲኖሩ የፈቀደላቸው እንደ አንድ ስደተኛ ግለሰብ እንጂ፤ የስደት መንግስት እንዳለው መሪ ቆጥሯቸው አልነበረም፡፡
ይሁንና ውሎ ሲያድር እንግሊዝና ጣሊያን ተቃቃሩ። ስለዚህ እንግሊዝ በምሥራቅ አፍሪካ የፋሽስት ኃይል ላይ እርምጃ የምትወስደው መቼ ይሆን? ከሚል ጥያቄ በቀር፤ እርምጃ መውሰዷ የማይቀር መሆኑ ተረጋገጠ። ያልታሰበው ሆኖ፤ ሁለቱ ሐገራት ወደ ጦርነት ገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ፤ እንግሊዝ እንደ ተራ ስደተኛ ታያቸው የነበሩት ንጉሥ፤ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ እሴት ያላቸው ሰው ሆኑ፡፡ ስለዚህ አፄ ኃይለ ስላሴን በእንግሊዝ አውሮፕላን ወደ ሱዳን እንዲበሩ አደረገች፡፡
እርሳቸው ስደት ከገቡበት ከ1936 ዓ.ም (እኤአ) ጀምሮ፤ በዱር በገደሉ ከጣሊያን ፋሽስታዊ ኃይል ጋር ሲፋለሙ የነበሩት የኢትዮጵያ አርበኞች ከአፄ ኃይለስላሴ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ጣሊያን፤ በምስራቅ አፍሪካ 200 ሺህ የሚደርስ እና በደንብ የታጠቀ እና የተሟላ አቅርቦት የሚያገኝ ኃይል ነበራት፡፡ የፀረ ፋሽስት ጦርነቱ በአብዛኛው በእንግሊዝ የጦር መኮንኖች ይመራ ነበር፡፡ በንጉሡ የሚመራው ጦር በተለይ ጎጃምን ነፃ በማውጣት ትልቅ ሚና የተጫወተ ሲሆን፤ አፄ ኃይለስላሴም ጃንዋሪ፣ 15፣ 1941 ዓ.ም የኢትዮጵያን ባንዲራ በኢትዮጵያ ምድር ላይ አውለበለቡ፡፡
ሆኖም አፄ ኃይለስላሴ፤ በእንግሊዝ ከሚመራው ጦር ቀድመው መዲናዋን የመቆጣጠር ክብር እና ዕድል አላገኙም፡፡ ይህን ክብር ያገኘው፤ ከሶማሌ የጁባ ወንዝ ምንጭ አካባቢ ከኪሲማዩ ተነስቶ፤ ከፌብሩዋሪ 14 እስከ ኤፕሪል 5 ባሉት ሰባት ሣምንታት ጉዞ መቋዲሾን አቋርጦ፣ ሐረርን ተሻግሮ አዲስ አበባ የገባው የደቡብ፣ የምዕራብ እና የምሥራቅ አፍሪካ ጥምር ጦር ነው፡፡
በሰባት ሣምንታት 1 ሺህ 850 ኪሎ ሜትር ተጉዞ አዲስ አበባ የገባው ጦር፤ በየቦታው ያገኘውን በርካታ የጣሊያን ጦር እየደመሰሰ፤ በርካታ የስንቅ እና ትጥቅ መጋዘኖችን እየተቆጣጠረ ዘለቀ፡፡
የኦስታው ዱክ አምባላጌ ላይ ተሸነፈ፡፡ በዚህ ጊዜ፤ እዛም - እዛም ያሉ የማዘዣ ጣቢያዎችን ከመቆጣጠር በቀር፤ ጦርነቱ በወሳኝ መልኩ ተጠናቅቆ ነበር፡፡ ይህ ፈጣን የድል ግስጋሴ፤ የዚህ ዘመቻ ወታደራዊ እንቆቅልሽ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ በቁጥር ትንሽ የሆነ ኃይል፤ በርካታ ቁጥር በነበረው የጦር ኃይል ላይ በአጭር ጊዜ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ድል እንዴት ሊጎናፀፍ ቻለ? የሚለው ጥያቄ፤ በርካታ ኃይል እና አስተማማኝ አቅርቦት ያለውን፤ እንዲሁም ስፍር ቁጥር የሌለው ለመከላከል ጦርነት ምቹ የሆነ መሬት የተቆናጠጠው የፋሽስት ጣሊያን ኃይል እንዲህ እንደ ቀላል የመበታተኑ ምስጢር የሞራል ውድቀት መሆኑን ወታደራዊ ጠበብት ይናገራሉ፡፡ የፋሽስት ጣሊያን ጦር፤ ከግማሽ ልብ ከፍ ባለ ወኔ ጦርነት ሲገጥም የታየው፤ ከረን ላይ በተካሄደው ጦርነት ብቻ ነበር፡፡ በመጨረሻ፤ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ከወሰደበት ጊዜ በጣም ባጠረ ጊዜ ተፈረካክሶ ከጥቅም ውጭ ሆነ፡፡
በድል ማግስት
ከዚህ በኋላ፤ አፄ ኃይለስላሴ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠበቁ፡፡ ፌብሩዋሪ 4፣ 1941 ዓ.ም (እኤአ) የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤደን በፓርላማው ፊት ቀርቦ፤ የእንግሊዝ መንግስት ነፃ የኢትዮጵያ መንግስት ዳግም እንዲመሰረት ፈቃደኛ መሆኗን እና የዚህ መንግስት ዙፋን የኃይለስላሴ መሆኑን ዕውቅና መስጠቷን ገለፀ፡፡ አፄ ኃይለስላሴ የውጭ መንግስታት ዕርዳታ እና ምክር ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ገለፀ፡፡
የእንግሊዝ መንግስት የንጉሡን የዕርዳታ እና ምክር ጥያቄ የተቀበለ መሆኑን ኤደን ጠቅሶ፤ እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስምምነት ለማድረግ የተለያዩ ሐገራት የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ስምምነት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስታወቀ፡፡ እንግሊዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ግዛት የማስፋፋት ፍላጎት እንደ ሌላት አመልክቷል። ከዚህ ሌላ፤ በኢትዮጵያ የሚካሔደው ወታደራዊ ዘመቻ፤ እንግሊዝ ወታደራዊ አመራር እና ውሳኔ የመስጠት ጊዜአዊ ሥልጣን እንዲኖራት ማድረግን የሚጠይቅ ሥራ እንደሆነ ገልጦ፤ ይህም ሥራ ከንጉሡ ጋር በመመካከር የሚፈፀም እና ሁኔታው በፈቀደ ፍጥነት እንግሊዝ ራሷን ከዚህ ኃላፊነት እንደምታወጣ አስታውቆ ነበር፡፡ እንግሊዝ ይህን ቃል የገባችው፤ ከጦርነቱ በፊት ሲሆን የጣሊያን የምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት እንደሚፈርስ በመገመት የወሰደችው ውሳኔ ነበር፡፡
አፄ ኃይለስላሴ ስደት ከወጡ ከ5 ዓመታት በኋላ መናገሻ ከተማቸው ከሆነችው አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ወዲያው ሚኒስትሮቻቸውን ሰይመው፤ በመዲናዋ እና በጠቅላይ ግዛቶቻቸው የመንግስት አስተዳደራቸውን እንደገና ለመመስረት ደፋ ቀና ማለት ያዙ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን፤ እንግሊዝ የራሷን አስተዳደር ለማፅናት ከፍተኛ ጥረት አደረገች፡፡ አንዳንዴም ከኢትዮጵያ መንግስት የበላይ የመሆን ሁኔታ ታሳይ ነበር፡፡
እንግሊዝ፤ በአስተዳደር ሥራው ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደረገችው ሰዎች ወታደሮች ብቻ መሆናቸውን ለማሳየት ብትሞክርም፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል በእንግሊዝ የቅኝ ግዛት አስተዳደር ውስጥ ተሳታፊ የሆኑና ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደላከች ግልፅ ነበር፡፡ ስለዚህ ነገሩ ያላማራቸው የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ እንግሊዛውያን ስጋታቸውን መግለፅ ያዙ፡፡ በተለይ በቅኝ አገዛዝ አስተዳደር ልምድ ያላቸው ባለሥልጣናት በማስተዳድሩ ተሳታፊ መሆናቸው፤ የእንግሊዝን ጉዳይ አሳሳቢ አድርጎት ነበር፡፡ ለረጅም ዘመን የዘለቀ ራስን በራስ የማስተዳደር እና የመንግስት አመራር ልምድ ባለው ወዳጅ ህዝብ ላይ የቅኝ አገዛዝ አስተዳደር ልምድ ያላቸውን ሰዎች መሰየሟ ሥጋት ያሳደረባቸው በርካቶች ነበሩ፡፡ በመሆኑም፤ በእንግሊዝ ፓርላማ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል፤ ‹‹የእንግሊዝ መንግስት ለኃይለስላሴ ዕውቅና የሚሰጠው እና የነፃ ሐገር መሪ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በፀረ ፋሽስት ትግሉ የእንግሊዝ መንግስት አጋር ሆና በጦርነቱ የተሰለፈች ሐገር ስለመሆኗ ዕውቅና የሚሰጠው መቼ ነው?›› የሚል ጥያቄ ይነሳ ጀመር፡፡ ‹‹ከጦርነቱ በፊት፤ የመጨረሻው ድል እስኪገኝ ድረስ እርሳቸውም ሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ የፋሽስት ኃይልን በጦር ለማንበርከክ ዝግጁ መሆናቸውን አፄ ኃይለስላሴ መግለፃቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ የእንግሊዝ መንግስት ይህን መርሳት አይገባውም›› በማለት የፓርላማ አባላት ጥያቄ ያነሱ ነበር፡፡
በመጨረሻም፤ የእንግሊዝ መንግስት ጃንዋሪ 19፣ 1942 ዓ.ም (እኤአ)፤ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር መፈራረሙን አሳወቀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኤደን ፌብሬዋሪ 3፣ 1942 ዓ.ም (እኤአ) በሰጠው መግለጫ እንዳሳወቀው፤ የዚህ ስምምነት አጠቃላይ ይዘት፤ የእንግሊዝ መንግስት ለኃይለስላሴ መንግስት ኦፊሴላዊ ዕውቅና የሰጠ መሆኑን፤ የ2.500.000 ፓውንድ ዕርዳታ መሰጠቱን፤ በወታደራዊ ተልእኮ ረገድ እና በሌሎች የተለያዩ መስኮች ምክር ለመለገስ ዝግጁ መሆኑን የሚያመለክት ነበር። ይህም እርዳታ ለኢትዮጵያ መንግስት የተሰጠው፤ እንግሊዝ በጦርነቱ ሂደት የኢትዮጵያን የጦር ማዘዣዎች እና የግንኙነት አውታሮች የተጠቀመች በመሆኑ፤ ይህን ውለታ ለመክፈል ታስቦ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ከእንግሊዝ ሌላ በዚህ ታሪክ ሁነኛ ሥፍራ ያላት ሐገር አሜሪካ ናት፡፡ አሜሪካ ለፋሽስት ጣሊያን የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ዕውቅና አልሰጠችም፡፡ እንዲያውም የአሜሪካ መንግስት፤ ከአፄ ኃይለስላሴ መንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመስረት ይፈልጋል። አሜሪካ ይህን ማድረግ የፈለገችው፤ ነገሩን በፍትህ ሚዛን አስልታ ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቅስ በአዲስ አበባ እና ቤሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የዲፕሎማቲክ መቀመጫ ማግኘት እና የቆንስላ ጽ/ቤቶችን በመክፈት ወኪሎቿን ማስቀመጥ፤ አካባቢውን የተመለከተ መረጃ ለማሰባሰብ በር እንደሚከፍትላት በማሰብ ነበር፡፡ አሜሪካ፤ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጥሩ ከበሬታ ነበራት፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ መቀመጫ ማግኘት ‹‹ከአላይድ ፓወር›› ጋር መልካም ግንኙት ለመመስረት ምቹ ሁኔታ እንዲሚፈጥርላት ተረድታለች፡፡
ፀሐፊው ሮበርት ጋሌ ውልበርት፤ ‹‹ኢትዮጵያ፤ የተመድ አባል ሐገር እና የዋሽንግተን ስምምነት ፈራሚ (ጃንዋሪ 2፣ 1942) ነች፡፡ ኃይለስላሴ እና የኢትዮጵያ አርበኞችም የፀረ-ፋሽስት ኃይልን ትግሉን አስቀድመው የተቀላቀሉ ናቸው፡፡ በወቅቱ የተመድ አባል የሆኑት ሃያ ስድስቱ ሐገራት፤ ‹‹ጦርነቱ የእኛም ጦርነት ነው›› የሚል አቋም ከመውሰዳቸው አስቀድሞ ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ ስለሆም፤ እነዚህ ሐገራት የኢትዮጵያን ውለታ በትንሹም ቢሆን ሊመልሱ የሚችሉት፤ እሷም እንደነሱ ነፃ ሐገር መሆኗን በመቀበል ነው፡፡ ይህን ማድረግም ብልህ ዲፕሎማሲያዊ ስትራተጂ ነው፡፡ ይህን በማድረግ ‹‹የአላይድ ፓወር›› የጥቁር ህዝቦችን እና በቅኝ ግዛት የሚማቅቁ ሐገሮችን ልብ ለማሸነፍ ይችላሉ›› ብሎ ነበር፡፡
አሜሪካ፤ እነጣሊያንን (አክሲስ ፓወርን) የሚያጠናክር ነገር እንዲፈጠር አትፈልግም፡፡ እንዲሁም፤ ሌላ ጦርነት ሊቀሰቅስ የሚችል ቅሬታ እንዲፈጠር አትሻም፡፡ በዋሽንግተን ለተፈረመው ስምምነትም ተገዢ መሆን ትፈልጋለች፡፡ ይህ የዋሽንግተን ስምምነት ኢትዮጵያ ነፃ ሐገር መሆንዋን የሚደግፍ ስምምነት ሲሆን በወቅቱ ‹‹የኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ ምን ይሁን?›› የሚለው ጥያቄ ሲመጣ፤ አነጋጋሪ ነጥብ ሆኖ የወጣው የድንበር ጉዳይ ነበር፡፡
በዚህ ረገድ በእንግሊዝ የተንፀባረቀው አስተሳሰብ በሦስት ዋና ዋና ጎራዎች የተከፈለ ነበር፡፡ አንደኛው ወገን፤ ሊበራል እና ፀረ ኢምፔሪያሊስት አቋም አራማጆችን የያዘ ነው፡፡ በዚህ ጎራ ያሉ እንግሊዛውያን፤ የኢትዮጵያ ድንበር ከ1935 ዓ.ም (ከጦርነቱ በፊት) የነበረውን ግዛት የሚያካትት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ይልቅስ፤ ኤርትራን፣ ምናልባትም የፈረንሳይ ሶማሌላንድን (ጅቡቲን) እንዲሁም የጣሊያን ሶማሌላንድን (ሰሜን ሶማሊያን) የሚያካትት ግዛት ሊሆን ይገባል የሚል አቋም ነበራቸው። ይህን አቋም የያዙት ወገኖች፤ ምክረ ሐሳባቸውን ሊደግፉ የሚችሉ በርካታ ጅኦግራፊያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ብሔረሰባዊ ጉዳይን በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ ‹‹ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ እና ከፍተኛ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም ያለው›› በሚል የሚጠቀስ ቡድን ደግሞ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ተስፋ በሚያሳጣ ሁኔታ እጅግ ኋላ ቀር ሐገር በመሆኗ፤ ከ1935 በፊት በነበረው ግዛቷ ላይ ሌላ ይጨመርላት የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት የሌለው ነው። ይህ ሊሆን አይገባም፡፡ እንዲያውም፤ አማርኛ ተናጋሪ እና ክርስቲያን ያልሆነውን ህዝብ ለብቻ በመነጠል፤ ነባር የአቢሲኒያ ግዛት በሆነው የሐገሪቱ ክፍል ለሚኖረው ህዝብ የይስሙላ ነፃነት ሰጥቶ በእንግሊዝ ሞግዚትነት እንዲተዳደር ማድረግ ያስፈልጋል›› የሚል አቋም የሚያራምድ ነበር፡፡ ይህ ምክረ ሐሳብ፤ ‹‹Hoare-Laval Plan›› በሚል የሚታወቀውን ዕቅድ እንደገና የሚጎትት እና መልሶ የሚያፀና ቢሆንም፤ ይህን አቋም የሚያራምዱ ወገኖች አፄ ኃይለስላሴ ‹‹ምክር እና ዕርዳታ›› ሊቀበሉ ይገባል የሚል አስተያየት በአፅኖት ያስተገባ ነበር፡፡ ሦስተኛው ወገን ደግሞ፤ ልቡ ለጣሊያን የሚራራ ነበር። እንደ ሻለቃ ፖልሰን ኒውማን ያሉ ለጣሊያን የቅኝ ግዛት ታሪክ ትልቅ ግምት የሚሰጡ ወገኖች፤ ‹‹ከጦርነቱ በኋላ ቢያንስ ኤርትራ እና ሶማሊያ እንደማስተዛዘኛ ለጣሊያን ሊመለስላት ይገባል›› ባዮች ነበሩ፡፡ ዋና ዋናዎቹ የሐሳብ ቡድኖች እነዚህ ቢሆኑም፤ ከሦስቱ ወደ አንዱ ሊደመሩ የሚችሉ አስተያየቶች ነበሩ፡፡
ከዚህ ሌላ፤ ከሰሃራ በታች ያለውን የአፍሪካ ምድር አንድ አድርገው የሚመለከቱ እና ከሰሃራ በታች ያለው የአፍሪካ ምድር፤ የደቡብ አፍሪካ ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይል ግዛት ሊደረግ ይገባል የሚል አቋም የያዙም ነበሩ፡፡ ከዚህ ሌላ፤ ‹‹የተባበሩት የአፍሪካ መንግስታት›› (United States of Africa) ይመስረት፤ ኢትዮጵያም የዚህ ግዛት አካል ትሁን የሚል አመለካከት የነበራቸው ወገኖች ነበሩ። አሁን ወደ እንግሊዝ እንመለስ፡፡
አንዳንዶች፤ እንግሊዝ የኢትዮጵያን ነፃ መንግስትነት ለመቀበል እንዲያ ያቅማማችው፤ ከጦርነቱ በፊት (1935) የነበረውን የኢትዮጵያ ግዛት እንዳለ ለመቀበል ባለመፈለጓ ነበር ይላሉ፡፡ አስቀድማ የጣሊያንን የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ስለተቀበለች፤ ‹‹እኔ ኢትዮጵያ ነፃ መንግስት ትሁን ስል፤ ቀደም ሲል የነበራትን ግዛት እንደ ያዘች ማለቴ አይደለም›› የሚል ማደናገሪያ ለማቅረብ ትችላለች፡፡ አሜሪካ እንዲህ የማድረግ ሐሳብ አልነበራትም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፤ በወቅቱ የተመድ አባል ሐገራት የነበሩት ሁሉ በፊርማቸው ያፀደቁት ‹‹አትላንቲክ ቻርተር›› የተሰኘው ሰነድ፤ ፈራሚዎቹ ሐገራት ምንም ዓይነት የግዛት ማስፋፋት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ የሚከለክላቸው ነበር። የድንበር ለውጥ የሚደረግ ከሆነም፤ ለውጡ በባለጉዳዩ ህዝብ ሙሉ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሚገባው የሚያዝ ስምምነት ነበር፡፡
የማትከፈል አንድ
አንደ መፅሔቱ ዘገባ፤ በወቅቱ የኢትዮጵያን ህዝብ በሐይማኖት እና በብሔር መስመር ከፋፍሎ አዲስ ካርታ የመፍጠር ፍላጎት ነበር፡፡ ሆኖም፤  የህዝቡ ስብጥር ሐይማኖት እና ብሔርን መሠረት ያደረገ ድንበር ለመፍጠር የሚያመች አልሆነም፡፡ ሌላው ቀርቶ በካርታ እንኳን ለመሳል እስኪያቸግር ድረስ ህዝቡ ተቀላቅሎ የሚኖር በመሆኑ መቸገራቸው አልቀረም፡፡ ታዲያ በወቅቱ በ‹‹ፎሪን ፖሊሲ›› መጣጥፍ ያቀረቡት ፀሐፊ፤ የብሔር እና የሐይማኖት ልዩነት በኢትዮጵያ ታሪክ ያላቸውን ሚና ከጠቀሰ በኋላ፤ የኢትዮጵያ ሁኔታ በምኒልክ፣ በይበልጥም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት እየተለወጠ መምጣቱን ያመለክታል፡፡ እንደ አብነት የጠቀሰውም፤ የልጅ ኢያሱን ጉዳይ ነው፡፡
የምኒልክ የልጅ ልጅ የሆኑት የልጅ ኢያሱ አባት (የወሎው ንጉስ ሚካኤል) መሠረታቸው ኢስላም መሆኑን የጠቀሰው ይኸው ፀሐፊ፤ ‹‹ልጅ ኢያሱ ወደ እስልምና አዘነበሉ በሚል ከሥልጣን የወረዱበት ሁኔታ ቢፈጠርም፤ በኢትዮጵያ የእስልምና እምነት መሠረት ያለው ሰው ከዙፋን መውጣቱ፤ ነገሮች እየተለወጡ መምጣታቸውን የሚያመለክት ነው›› ይላል፡፡
አያይዞም፤ በተለይ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የመንግስት ሥልጣን መያዝ መጀመራቸውን የሚጠቅሰው ይህ ፀሐፊ፤ የኢትዮጵያ መድህን የሚገኘው በዚህ ጎዳና እንደሆነ ይናገራል፡፡ ጠቅላላውን የኢትዮጵያ ግዛት የሚያቅፍ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ገና እንዳልዳበረ ጠቅሶ፤ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ይህን ስሜት በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና መጫወቱን ይገልፃል፡፡
ፀሐፊው፤ ጣሊያን ከምሥራቅ አፍሪካ መባረሯን ተከትሎ፤ የድንበር ጉዳይ በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚገኙ (እንደ ኤርትራ እና ሶማሊያ ያሉ የጣሊያን ነባር የቅኝ ግዛት) ሐገሮችን ጉዳይ እንደሚጎትት በመግለፅ፤ የጅቡቲም ጉዳይ ምላሽ የሚጠይቅ ነገር መሆኑን ያወሳል። የተጠቀሱትን ሐገራት ጨምሮ ህዝቡ በተበታተነ አኳኋን በሰፈረባት እና በእንግሊዝ ሞግዚትነት የምትተዳደረውን ‹‹ሱማሌ - ላንድ›› የሚያካትተው ጅኦግራፊያዊ ክልል፤ መልክዐ ምድራዊ እና ብሔረሰባዊ ትስስር ስላለው፤ አካባቢው እንደ አንድ ሰፊ ግዛት ሊታይ የሚችል እንደሆነ በመጠቆም፤ ከሞላ ጎደል ‹‹ጎነ - ሦስት›› የሆነ ቅርፅ የሚይዘው ይህ ክልል፤ ኩታ ገጠም ሆኖ ከሚገኘው አካባቢ ተለይቶ ሊታይ የሚችል ልዩ ባህርይ እና መልክ ያለው ግዛት ነው ይላል፡፡ ከመልክዐ ምድራዊ አንድነት በተጨማሪ፤ ይህ ግዛት ከፍተኛ ብሔረሰባዊ (?) ወጥነት (ethnic homogeneity) የሚታይበት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከሱዳን ጋር ያለውን ድንበር ተከትሎ ከሚኖሩ ህዝቦች በስተቀር፤ በዚህ ግዛት የሚኖሩት ህዝቦች፤ አንትሮፖሎጂስቶች ‹‹ኢትዮፒክ›› (Ethiopic type) የሚሉት ዓይነት አካላዊ ገፅታ ያላቸው ህዝቦች የሚኖሩበት መሆኑን በማንሳት፤ ይህ ክልል በአንድ አንዲጠቃለል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳል፡፡
ፀሐፊው በማያያዝ፤ ‹‹ከጦርነቱ በኋላ ለአፍሪካ የድንበር ጉዳይ እልባት ለመስጠት ሙከራ ሲደረግ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከጦርነቱ በፊት ከነበራት ግዛት ሰፋ ያለ የድንበር ጥያቄ እንደምታቀርብ አይጠረጠርም›› ይላል፡፡ አክሎም፤ ‹‹ንጉሡ ገና አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት፤ በሎንዶን የኢትዮጵያ ሚኒስትር (?) ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ዶ/ር ወርቅነህ ማርቲን፤ የበፋሽስት ጣሊያን ጦር በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ላደረሰው የከፋ ጭፍጨፋ ካሳ ይሆን ዘንድ፤ የአሰብ እና የምፅዋ ወደቦች እንዲሁም በሁለቱ ወደቦች መካከል ያለው የባህር ዳርቻ፤ አሁን ኤርትራ በሚል የሚጠራውን የሐማሴን ግዛት ጨምሮ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ይገባል፡፡ በእርግጥ፤ የህዝቡ ፍላጎት ተጠይቆ፤ የኢትዮጵያ ኤምፓየር ነፃ እና እኩያ አባል ለመሆን እንፈልጋለን የሚል ውሳኔ ካሳለፉ የጣሊያን ሱማሌ - ላንድ ግዛት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካተት መደረግ አለበት ሲሉ ፅፈዋል›› በማለት አትቷል፡፡
እንዲያውም፤ አንዳንድ የእንግሊዝ የአደባባይ ሰዎች (publicists) ‹‹የፈረንሳይ ሱማሌላንድ የተባለችው ጅቡቲ፤ ለማዕከላዊ እና ደቡባዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ምቹ የባህር በር ሆና የምታገለግል ስለሆነ፤ ለኢትዮጵያ ልትሰጥ ይገባል›› የሚል ሐሳብ ያራምዱ እንደ ነበረ ገልጧል፡፡
‹‹ኤርትራን ወይም ቢያንስ የኤርትራን ተራራማ ክፍሎችን በተመለከተ ኢትዮጵያ የምታቀርበውን የይገባኛል ጥያቄ ውድቅ ማድረግ አስቸጋሪ ነው›› የሚለው ፀሐፊው፤ ‹‹Round Table›› የተሰኘ አንድ ‹‹ሦስት - ወራዊ›› መፅሔት፤ የሴፕቴምበር 1941 ዕትም፤ ‹‹የቀይ ባህር እና የህንድ ውቂያኖስ ዳርቻዎች በኢትዮጵያ ዘንድ አመኔታ ሊፈጥር እና ለወጪ-ገቢ ዕቃዎች አስፈላጊውን አገልግሎት ሊሰጥ በሚችል አንድ መንግስት ሥር እንዲተዳደር ማድረግ ይገባል›› በሚል ያሰፈረውን ሐሳብ ይቃወማል፡፡
ተቃውሞውን ሲገልፅም፤ ‹‹ይህ ምክረ ሐሳብ ቢያንስ ቢያንስ ቀይ ባህርን በተመለከተ የተሳሳተ ምክር ይመስላል፡፡ የቀይ ባህር ዳርቻ፤ ከምፅዋ፣ ከአሰብ ከሌሎች ጥቂት ትናንሽ የሆኑ መንደሮች በቀር ሰው የማይኖርበት ነው፡፡ አሰብ እና ምፅዋ ትርጉም የሚኖራቸው ለደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል ወደብ ሆነው ማገልገል ከቻሉ ብቻ ነው፡፡ ምፅዋን ከመሐል ሐገር መለየት ኢኮኖሚያዊና ጅኦግራፊካል ሐጢያት ነው (geographic and economic absurdity)፡፡ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትርጉም እንዲኖራት ከተፈለገ፤ ወደብ ሊኖራት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት አለማድረግ ሊያሳካው የሚችለው ትርጉም ያለው ግብ፤ ሐገሪቱን ከፊል የቅኝ ግዛት ሁኔታ ውስጥ ማኖር ብቻ ነው›› በማለት አትቷል፡፡
‹‹የጅቡቲም ነገር ከዚህ የተለየ አይደለም›› የሚለው ይኸው ፀሐፊ፤ ‹‹ ፈረንሳይ በፓስፊክ እና በህንድ ውቂያኖስ ያላትን ግዛት ይዛ መቀጠል ከቻለች ጅቡቲ ምናልባት entrepôt ሆና ማገልገሏን ትቀጥላለች። ከወደቡ ውጭ ያለው የፈረንሳይ ሶማሌላንድ ምድር ወደ ኢትዮጵያ ሊጠቃለል ይችላል፡፡ ምክንያቱም በዚህ አካባቢ የሚኖረው ህዝብ በአጎራባች ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ብሔሮች (አፋር እና ሶማሌ) ጋር አንድ ዓይነት ባህል ያላቸው ናቸው›› ይላል፡፡
ይህን ባህላዊ፣ ብሔረሰባዊ እና መልክዐ ምድራዊ አንድነት አንዲነጣጠል ማድረግ፤ ፖለቲካዊ ብልህነትን የማያንፀባርቅ፤ እንዲሁም ከመልክዐ ምድር አኳያ የማይሞከር ተግባር መሆኑን በመጥቀስ፤ ተፈላጊውን አንድነት ለማምጣት ይህን ተፈጥሮአዊ አንድነት በፖለቲካዊ አንድነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ያትታል፡፡
ይህ ዓላማ እንዲሳካ አስተዋይ እና በሳል አመራር እንደሚጠይቅ፤ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ዕርዳታ እና ምክር እንደሚያስፈልገው የሚናገረው ፀሐፊው፤ ‹‹በቅርቡ በኢትዮጵያ እና የእንግሊዝ መንግስታት መካከል ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ስምምነት ተፈርሟል፡፡
በዚህ ስምምነት የእንግሊዝ ዳኞች በኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች ያስችላሉ፤ የእንግሊዝ አማካሪዎች ለንጉሱ አስተዳደር ምክር ይለግሳሉ፤ የእንግሊዝ የጦር መኮንኖች ለጦር ሠራዊት እና ለፖሊስ ሠራዊት ስልጠና ይሰጣሉ። ስምምነቱ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ በሐገሪቱ ግዛት ለሚከሰት ጦርነት የእንግሊዝ መንግስት ሙሉ ሥልጣን እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ይህ ሰፊ የአድራጊ ፈጣሪነት ሥልጣን፤ ኢትዮጵያን የእንግሊዝ ዲፋክቶ የሞግዚት አስተዳደር ያደርጋታል›› ሲል ፅፎ ነበር፡፡
ሆኖም ፀሐፊው እንደ ገለፀው፤ ‹‹በቅኝ ግዛት ከቆዩ ወይም ለረጅም ዘመን በውጭ አስተዳደር ሥር ከቆዩ ህዝቦች በተለየ ሁኔታ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ትዕግስት የሚኖረው፣ ልቡ የሚሸነፈው እና የሚተባበረው ከራሱ በተውጣጡ ሰዎች ለተቋቋመ መንግስት ብቻ ነው›› በማለት ፅሁፉን አጠቃሏል፡፡  

Published in ህብረተሰብ

በሕፃናት አስተዳደግ ዙሪያ ጥናትና ምርምር ያደረጉ አንዳንድ ምሁራን፣ የሰው ልጅ ማንነት ወይም የወደፊት ሰብዕና የሚቀረፀው ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ባለው ዕድሜ ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የለም ከሁለት እስከ ሰባት ዓመት ነው ይላሉ፡፡
የሁለት ዓመት ልዩነት ብዙ አያከራክርም፡፡ ዋናው ነጥብ የሕፃናት የወደፊት ማንነት የሚቀረፀው በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ መሆኑን መገንዘብ ነው፡፡ ልጅ ከበላ፣ ከጠጣ፣ ከለበሰ ምን ያስፈልገዋል? የሚለውን ባህላዊና ልማዳዊ የልጆች አስተዳደግ በዘመናዊ ዘዴ መተካት የግድ ነው፡፡ ልጅ ምንም አያውቅም? በማለት ሰብዕናቸውን የሚጐዳ ነገር ከመናገርና ከመተግበርም መቆጠብ አለብን፡፡ የ6 ወር ሕፃን፣ ቤተሰቦቿ፣ በሞባይል ሲያወሩ አይታ ሞባይል ወይም ሌላ ነገር አንስታ ወደ ጆሮዋ ስትወስድ፣ የ2 ዓመት ልጅ ወላጆቹ የማይችሉትን የሞባይል ጌም አቀላጥፎ ሲጫወት ቢያዩ አይገረሙ። ሕፃናት ብዙ ያውቃሉ፡፡ ቢያውቁም ግን መልካሙን የሚያሳያቸውና ወደ ጥሩ ነገር የሚመራቸው ይፈልጋሉ፡፡
ሕፃናት፣ ከወላጆች ቀጥሎ የሚያገኙት አሳዳጊ ሞግዚቶችን ነው፡፡ ትንሽ ከፍ ብለው አፀደ ሕፃናት ሲገቡ ደግሞ የአፀደ ሕፃናት መምህራንና ሞግዚቶች ይቀበሏቸዋል፡፡ እነዚህ ሞግዚቶችና መምህራን ሕፃናቱን በጥሩ መንገድ ለመምራትና የወደፊት ማንነታቸውን ለመቅረፅ፣ የልጆችን አስተዳደግና ሥነልቡና መማርና ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ችግር በአንዳንድ አፀደ ሕፃናት ይታያል፡፡
አብ ሁለገብ ማሠልጠኛ ማዕከል በደፈናው ችግሩ እንዳለ ከመግለፅ ባሻገር የችግሩ ስፋት ምን ያህል እንደሆነ፣ መምህራንና ሞግዚቶች ምን ዓይነት በሳይንስ የተደገፈ ሥልጠና እንደወሰዱ ለማወቅ በሕፃናት አስተዳደግ፣ ክብካቤ፣ ክትትል፣ አመጋገብ፣ ጤና፣ ሥነልቦና… ማስትሬትና ዶክትሬት ባላቸው ምሁራን መመዘኛ መስፈርቶች አዘጋጅቶ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ባሉ አፀደ ሕፃናት ጥናት ማድረጉ የማዕከሉ  የሥልጠና ኃላፊ አቶ መሐመድ ሰዒድ ተናግረዋል፡፡
በጥናቱ ያገኘነው ውጤት ከገመትነው በላይ ነበር ያሉት አቶ መሐመድ፤ በአገሪቷ፣ በመንግሥትም ሆነ በግል ለአፀደ ሕፃናት ሞግዚቶችና መምህራን ሥልጠና የሚሰጥ ተቋም ስለሌለ፣ ሞግዚቶቹ በልምድ ከሚያውቁትና ከሥራ መምሪያ ውጭ ሳይንሳዊ ሥልጠና እንዳላገኙ ማረጋገጥ ቻልን፡፡ የነገ አገር ተረካቢ ሕፃናት ሞግዚቶችና መምህራን ሳይንሳዊ ሥልጠና ቢያገኙ ጥሩ መሠረት ይሆኗቸዋል በማለት የጥናት ውጤቱን ለየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አቀርብን ብለዋል፡፡
ከመስተዳደሩ ያገኙት ግብረ መልስ አበረታች ስለነበር በዚህ ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት ለማጥበብና የዜግነት ግዴታቸውን ለማበርከት ፕሮጀክት ቀርፀው፣ ከት/ሚር የሞግዚቶች ሥልጠና ጋር አቀናጅተው ሳይንሳዊ ሥልጠና መስጠት እንደጀመሩ ባለፈው እሁድ ለ2ኛ ጊዜ በሞግዚትና በአፀደ ሕፃናት ረዳት መምህርነት ያሰለጠኗቸውን 126 ተማሪዎች ባስመረቁበት ወቅት ገልፀዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር በየካ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ አፀደ ሕፃናት ት/ቤቶች ለተውጣጡ 200 ሞግዚቶችና ረዳት መምህራን የ3 ወር ሥልጠና ሰጥተው በሰርቲፊኬት ማስመረቃቸውን ጠቅሰው፣ የ2ኛ ዙር ሠልጣኞች ከየካ፣ ከላፍቶና ከቦሌ ክፍለከተማ አፀደ ሕፃናት ት/ቤቶች የተውጣጡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ማዕከሉ የሚሰጠው ሥልጠና በሕፃናት ሥነ ልቡና (ሳይኮሎጂ)፣ በትምህርት አሰጣጥ፣ በሕፃናት አያያዝና እንክብካቤ፣ በንፅህና አጠባበቅ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ዕርዳታ (ፈርስት ኤይድ) አሰጣጥ፣ በሕፃናትና በሞግዚቶች መካከል መኖር ስላለበት ትስስር (ፍቅር) ሲሆን ኮርሶቹ የሚሰጡት ጥናቱን ባካሄዱት፣ ኮርሶቹን ባዘጋጁትና በዘርፉ ጥልቅ እውቀት ባላቸው ምሁራን እንደሆነ ታውቋል።
ሠልጣኞቹ ወደ እኛ ሲመጡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሲኖሩ የለመዱትንና ያዳበሩትን ልማድ ይዘው ነው ያሉት አቶ መሐመድ፤ ይዘውት የመጡትን ባህላዊና ልማዳዊ ጐጂ የሕፃናት አስተዳደግ በሳይንሳዊ ስልጠና ከውስጣቸው እንዲፍቁ አድርገን እናሠለጥናለን፡፡ እያንዳንዱ ክህሎት የሚዳብረው በሂደት ስለሆነ ሁሉም ሠልጣኞች በሂደት ተመሳሳይ እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ሕፃናቱም የወላጆቻቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ባህርይ ይዘው እንደሚመጡ ኃላፊው ጠቅሰው፣ ሞግዚቶቹ፣ እነዚህን የተለያየ ባህርይ ያላቸውን ሕፃናት እንዴት በፍቅር ቀርበውና ፍቅር ሰጥተው እንዲወዷቸውና እንዲቀርቧቸው ማድረግ አለባቸው፤ አንዳንድ ሕፃናት በትንሽ ነገር ሆድ እንደሚብሳቸው እንደሚነጫነጩ ጠቅሰን ሌላው ደግሞ ተንኳሽና ተደባዳቢ፣ አንዳንዱ ጐበዝ፣ ሌላው ሰነፍ፣ ስለሚሆነው ምን ማድረግና እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው እናስተምራቸዋለን በማለት አስረድተዋል፡፡
ከየካ ክፍለ ከተማ የመጣችው መሠረት ብርሃኑ ዕድሜ 30 ሲሆን በመምህር ረዳትነት ነው የለጠነችው። በካይዘን ማኔጅመንት ፅንሰ ሐሳብ መሰልጠኗን ጠቅሳ ሕፃናቱን እንዴት መንከባከብና ችግሮቻቸውን እንዴት መረዳት እንዳለባቸው ግንዛቤ ማግኘቷ ገልጻለች። ከዚህም በላይ ልጆች ምንም አያውቁም የሚባለው ትክክል ስላልሆነና ልጆች ብዙ ነገር ስለሚያውቁ ትኩረት መስጠት እንዳለባት መረዳቷን ተናግራለች፡፡
“ሕፃናት ከቤት እንደወጡ የምንረከባቸው እኛ ነን፡፡ ከሥልጠናው ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ፡፡ ሕፃናት የኅብረተሰቡን መልካም እሴቶች እንዲያውቁ አደርጋለሁ” ያለችው በሞግዚትነት የሠለጠነችው የ35 ዓመቷ ሐና ዘውዴ ናት፡፡ ሕፃናት አስቸጋሪ መሆናቸውን በማስተምርበት ት/ቤት አውቀዋለሁ፡፡ ዕድሜያቸው ሲጨምር ባህሪያቸው እንደሚለዋወጥ ከዚህ ስልጠና ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህ ሁሉንም በትዕግሥት እየተቀበልኩ በፍቅር አስተናግዳቸዋለሁ ብላለች።
ወ/ሮ ይመኙሻል ሰብስቤ የ50 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ ከልጆች ጋር መዋልና የገቢ አቅማቸው አነስተኛ የሆኑ ቤተሰብ ልጆችን ማስተማር ይወዳሉ። የኮንዶሚኒየም ዕጣ ደርሷቸው አሁን የሚኖሩት ሰሚት አካባቢ ነው። ሰፈር ከመልቀቃቸው በፊት ቀበና አካባቢ ወላጅ የሌላቸውንና የድሃ ልጆችን በራቸው ላይ መጠለያ ሠርተው ለ8 ዓመት በነፃ ማስተማራቸውን ተናግረዋል፡፡ አንዲት የድሃ ልጅ እናቷ መንገድ ላይ እየለመኑ የሚያገኙት ስለማይበቃቸው አንዳንድ ጊዜ እሳቸው ጋ እየሄደች ትመገብ ነበር፡፡ እናቷ ሲሞቱ ልጅቷን እቤታቸው አስገብተው እያስተማሩ 9ኛ ክፍል እንደደረሰችላቸው ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል በሕፃናት መምህርትነት ሰልጥነው ስለነበር አሁን በሚኖሩበት ሰሚት አካባቢ ሸቡ ኤጀርሳ በተባለ ት/ቤት እያስተማሩ ነው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ይሰጣል ሲባል የእውቀት ትንሽ የለውም በማለት ሥልጠናውን ጀምረው የማያውቁትን ከፍተኛ እውቀት መገብየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ልጆች በዕድሜ ደረጃ መያዝ እንዳለባቸው፣ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ማወቅ፣ እንዴት መንከባከብና ንፅህናቸውን መጠበቅ ከወላጅ ይበልጥ ሞግዚት መከታተል እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ የምግብ መያዣ ዕቃቸው ንፁህ መሆኑንና ያለመሆኑን መቆጣጠር፤ በሽታና ጠረን ማወቅ እንዳለባቸው፣ የልጆቹ ባህርይ፣ የምግብና የጨዋታ ፍላጐታቸው ምን እንደሆነ ማጥናት እንደሚገባቸው፣ በካይዘን ማኔጅመንት፣ በሕፃናት አስተዳደግና በሳይኮሎጂ ትምህርት ያገኙ በርካታ እውቀት መሠረታዊና ለሥራቸውም የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሌላው ጠቃሚ ትምህርት የሕፃናት ጤና ስለሆነ ልጆች እጃቸውንና ጣቶቻቸውን እንዴት መታጠብ እንዳለባቸው፣ ሕፃናት ሳሙና በእጃቸው ላይ መፈግፈግ ስለማይችሉ ፈሳሽ ሳሙና መጠቀም እንዳለባቸው፣ በት/ቤቱ ፈሳሽ ሳሙና ባይኖር እንኳ ሳሙናውን ቀጥቅጠን በፈላ ውሃ ውስጥ በመበጥበጥ በሃይላንድ ውሃ መያዣ ውስጥ ጨምረን በመክደን ክዳኑን በስተን ፊጭጭ በማድረግ ልጆች በሰልፍ መጥተው እጃቸውንና አፋቸውን እንዲታጠቡ ማድረግን የተማርኩት እዚህ ማሰልጠኛ ነው በማለት ከሥልጠናው ያገኙትን እውቀት አስረድተዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ያሉት አፀደ ሕፃናት ሙያው ባላቸው ሞግዚቶች እንዲጠቀሙ የማድረግ የአጭር ጊዜ ዕቅድ አለን ያሉት የሥልጠና ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ አሳየ ተክሉ፤ በረዥም ጊዜ ዕቅዳቸው በ2012 ዓ.ም በመላ አገሪቷ ያሉ አፀደ ሕፃናት የሙያው ባለቤት በሆኑ መምህራንና ሞግዚቶች እንዲሰለጥኑ ማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል።
አቶ አሳየ ሥልጠናውን ሲጀምሩ ሁለት ችግሮች አጋጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አንደኛው ዘርፉ አዲስ በመሆኑ ከቴክኒክና ሙያ ጽ/ቤት ባለሙያዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የአፀደ ሕፃናት መምህራንና ሞግዚቶች ሳይንሳዊ ሥልጠናና ብቃት ያስፈልጋል የሚለውን ሃሳብ ለማስረፅና ለማሳመን ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸው ነበር፡፡
ሌላኛው ችግር አፀደ ሕፃናት ማስተማሪያ ት/ቤት ባለቤቶች የፈጠሩባቸው ችግር ነበር፡፡ ይኼውም ሠራተኞቻቸው ሳይንሳዊ ሥልጠና ካገኙ ባለሙያ ስለሚሆኑ የተሻለ ክፍያ ፍለጋ ጥለውን ይሄዳሉ በሚል ስጋት ሰራተኞቹ ወደ ስልጠናው እንዳይሄዱ ያደርጉ ነበር፡፡ ሥልጠናው ከተጀመረ በኋላ ከሁለቱም ክፍሎች ያገኙት ምላሽ ጥሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡         

Published in ህብረተሰብ
Page 12 of 19