1. አዛውንቱን አባት እና ሴት ልጃቸውን ያናከሰ የፈረንሳይ የፖለቲካ ‘ድራማ’
“[አባቴ] አገር ምድሩን ካላቃጠልኩ ሞቼ እገኛለሁ የሚል መንፈስ ተጠናውቶታል። ከፓርቲ መሪነት ከወረደ በኋላ ፓርቲያችን በፍጥነት እያደገ ነው። ይሄም በቅናት ስሜት ያሳርረዋል” - በፈረንሳይ የፒኤፍ ፓርቲ መሪነትን ከአባቷ የተረከበችው ሜሪን ለፔን የተናገረችው ነው። ከሰሞኑ አባቷን ከፓርቲ አባልነት እንዲባረሩ አድርጋለች።
“እዚህ ያደረስኳት እኔ እንደሆንኩ ዘንግታለች። ተቃናቃኝ ፓርቲዎች ፊትለፊት ነው ጥቃት ሲሰነዝሩብኝ የነበረው። ይህች ግን፣ ከጀርባ አድብታ ወጋችኝ። ካላስገደለችኝ በቀር ፈፅሞ ሰላም እንደማልሰጣትና እንደማልተኛላት ማወቅ አለባት” - የፓርቲው መስራች አዛውንቱ ለፔን፣ ስለ ልጃቸው የተናገሩት ነው።
2. ስልጣን ተቀራምተው አገር ለማመሳቀል የሚናቆሩ የግሪክ ኮሙኒስት ፓርቲዎች።
“የትምህርት ቤትና የዩኒቨርስቲ አስተዳደር፣ በተማሪዎች ስር መሆን አለበት። መምህራንና ሰራተኞች ለተማሪ ይታዘዛሉ” - የትምህርት ሚኒስትሩ።
“ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች፣ ተበዳይ እንጂ አጥፊ አይደሉም። ጥፋቱ የሕብረተሰቡ ነው። ወንጀለኞች፣ መከሰስ ሳይሆን መካስ አለባቸው” - የፍትህ ሚኒስትሩ።    
3. ትልልቆቹ ፓርቲዎች በአቅመቢስነት የተብረከረኩበት የእንግሊዝ ምርጫ
በሰሞኑ የእንግሊዝ ምርጫ፣ ትልልቆቹ ፓርቲዎች (ቶሪ እና ሌበር) መላ ጠፍቷቸው ሲወራጩ ሰንብተዋል። “የማሸነፍ ተስፋ የላቸውም፤  ምን አይነት መንግስት እንደሚመሰርት ለማወቅ ያስቸግራል” የሚሉ መላምቶች ሊናፈሱ ከቆዩ በኋላ፤ በሐሙሱ ምርጫ የዴቪድ ካሜሮን ቶሪ ፓርቲ አሸንፏል፡፡ ከግማሽ በላይ የፓርላማ ወንበሮችን ተቆጣጥሯል፡፡ ከመራጮች ያገኘው የድጋፍ ድምፅ ግን 37% ብቻ ነው፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ በምርጫው ላይ የሚሳለቅ ሰው በምድረ አውሮፓ አልታየም። ሰበብ እየፈለጉ በእንግሊዝ ላይ ለመሳለቅ የሚሯሯጡ አንዳንድ የፈረንሳይ ፖለቲከኞች እንኳ፣ እንደወትሯቸው  ለማፌዝ አልተሽቀዳደሙም። ወደው አይደለም። የፈረንሳይ ፖለቲካም እንደወትሮው አይደለም። እየተናጠ ነው።  
በእንግሊዝ ስልጣን ላይ የሚፈራረቁት ሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች (ግራ ዘመሙ ሌበር ፓርቲ እና ቀኝ ዘመሙ ኮንሰርቫቲቭ ቶሪ ፓርቲ)፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደማጭነታቸው ቀንሷል። የዛሬን አያድርገውና፣ 90 በመቶ ያህል መራጮች፣ ለቶሪ ወይም ለሌበር ፓርቲ ነበር የድጋፍ ድምፃቸውን የሚሰጡት። ዛሬ ግን፣ የሁለቱ ለዘብተኛ ፓርቲዎች ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ከመምጣቱ የተነሳ፤ አንዳቸውም 35 በመቶ የሚደርስ የድጋፍ ድምፅ ለማግኘት ተስኗቸዋል።
የግል ማንነትንና የሚጠሉ የዘርና የ“ባህል” አምላኪዎች
በተቃራኒው ከ2% በላይ ድጋፍ ያልነበረው ‘ዩኬአይፒ’ የተሰኘው ብሔረተኛ ፓርቲ፣ የደጋፊዎቹን ቁጥር ወደ 13 በመቶ ገደማ አሳድጓል። በግል ነፃነት ላይ የተመሰረተ የካፒታሊዝም ስርዓት ላይ ፅኑ ተቃውሞውን ሲገልፅ፤ “ከግል ጥቅማችሁ በፊት የአገራችሁን ጥቅም አስቀድሙ” በማለት የፋሺዝም መፈክር ያስተጋባል - ዩኬአይፒ። “ኢትዮጵያ ትቅደም” ከሚለው የደርግ መፈክር ጋር ይመሳሰላል። “ጀርመን ትቅደም” የሚለው የናዚዎች መፈክርንም ማስታወስ ይቻላል፡፡ የሕዝብ ስሜት ለማነሳሳት “የውጭ ሃይሎች” ላይ ጣቱን የሚቀስረው ዩኬአይፒ፣ የአውሮፓ ህብረትንና ስደተኞችን በጠላትነት ይፈርጃል፡፡  ሁሉም ዘረኛ ፓርቲዎች ዘንድ የሚዘወተር የተለመደ ዘዴ ነው፡፡  ሰዎችን በግል ማንነታቸው ከመመዘን ይልቅ፤ በተወላጅነት የዘር ሃረግ እየቆጠርን “ባዕድ” እና “ወገን” በሚል እንድንቧደን ይፈልጋሉ።
የእንግሊዝ ፖለቲካ የተመሳቀለው ግን፣ በዚህ ብቻ አይደለም። የፓርላማ  ወንበሮችን ለማሸነፍ አቅም ያልነበረው ሌላ ብሔረተኛ ፓርቲም፣ በጥቂት አመታት ውስጥ ገናና እየሆነ መጥቷል - SNP፡፡ ስኮትላንድን ከእንግሊዝ የመገንጠል አላማ ያነገበው ይሄው ፓርቲ፤ እንደ አብዛኞቹ ብሔረተኞች ወደ ፋሺዝም ያዘነበለ ፀረ ካፒታሊዝም መፈክር ማራገቡ አይገርምም። “ከግል ጥቅማችሁ በፊት የስኮትላንድን ጥቅም አስቀድሙ” ይላል። “ብሔር ብሔረሰብ ይቅደም” እንደማለት ልትቆጥሩት ትችላላችሁ። የሕዝብን ስሜት ለማነሳሳትም፣ እንግሊዝንና ሌሎች “የውጭ ሃይሎችን” በጠላትነት ይፈርጃል። ለምን? ሰዎችን በግል ማንነታቸው ከመመዘን ይልቅ፣ በጅምላ “የብሔረሰብ ተወላጅ” እና “ባዕድ” እያሉ በማቧደን፣ የአንደኛው ቡድን ገዢ ለመሆን ይመኛሉ። በሰሞኑ ምርጫም  ፓርቲው ከ55 በላይ የፓርላማ ወንበሮችን ለማሸነፍ ችሏል፡፡
በጥረት መበልፀግንና የግል ንብረትን የሚጠሉ የምፅዋትና የዝርፊያ አምላኪዎች
በእንግሊዙ ምርጫ፤ ከፋሺስት ዘመም ብሔረተኛ ፓርቲዎች በተጨማሪ፣ ወደ ኮሙኒዝም የተጠጉ ፓርቲዎችም በተወሰነ ደረጃ ደጋፊዎችን ለማበራከት ችለዋል። “ከግል ጥቅማችሁ በፊት የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም ወይም የብዙሃኑን ጥቅም አስቀድሙ” የሚል ዲስኩር በመለፈፍ የካፒታሊዝም ቀንደኛ ጠላት እንደሆኑ የሚገልፁት እነዚሁ ሶሻሊስት ፓርቲዎች፤ “ነፃነቴ ይከበር” ብሎ ለሚጋፈጣቸው ሰው ምን አይነት ምላሽ ይሰጣሉ? “ይሄ የግል ሃሳብ ነው” ብለው ያጣጥሉታል።
ምናልባት ገፍቶ የሚከራከራቸው ሊኖር ይችላል። “መቼም የሕዝብ የጋራ አእምሮ የለም፤ የግል ሃሳቤን እንጂ ሌላ ምን አይነት ሃሳብ ልገልፅ እችላለሁ? የጋራ አእምሮ ስለሌለ’ኮ ነው፣ ሰዎች በየግላቸው የምርጫ ድምፅ የሚሰጡት” ብሎ ቢከራከራቸውስ? ሶሻሊስቶቹ፣ በዚህ ክርክር ብዙም አይደናገጡም። የሕዝብን ስሜት ለማነሳሳት የሚረዳ የተለመደ ዘዴ ይጠቀማሉ - ባለሃብቶችንና የቢዝነስ ድርጅቶችን በጠላትነት መፈረጅ!
“የግል ሃሳብና አቋም መያዝ ትችላለህ፤ ግን የሰፊውን ሕዝብ ፍላጎትና የብዙሃኑን ጥቅም አይወክልም። የያዝከው ሃሳብ ከከበርቴው ቡድን የሚመነጭ እንጂ፤ ዝቅተኛውንና ድሃውን የሕብረተሰብ ቡድን አይወክልም” በማለት ዝም ያሰኙታል።
አንደኛ፣ በነሱ ቤት፣ አንድ ሃሳብ ትክክል ወይም ስህተት የሚሆነው፣ በቁጥር ብዛት ወይም በቡድን ትልቅነት ነው። የግሪኩ የትምህርት ሚኒስቴር፣ “የዩኒቨርስቲ አስተዳደር በተማሪዎች ስር መሆን አለበት” የሚሉትም በዚህ ምክንያት ነው - የተማሪዎች ቁጥር ብዙ ስለሆነ፣ “ተማሪ” በሚል አንድ ላይ ከተቧደነ ትልቅ ስለሚሆን ነው።
ሁለተኛ፣ በሶሻሊስቶቹ እምነት፣ የሰው ሃሳብና ድርጊት የሚቃኘው በእያንዳንዱ ሰው ዝንባሌና ምርጫ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚና በኑሮ ደረጃው ነው - በ“መደብ”። የግሪኩ የፍትህ ሚኒስትር፣ “ወንጀለኞች ጥፋተኛ አይደሉም። ክስ ሳይሆን ካሳ ይገባቸዋል” የሚል ዲስኩር የሚለፍፉት ለምን ሆነና? ምን እያሉ እንደሆነ በጥንቃቄ አስተውሉ።
“ወንጀለኞች... በሰው ላይ ድብደባ፣ ዝርፊያና ግድያ የሚፈፅሙት... በክፋት ሳይሆን በድህነት ምክንያት ነዋ። በድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ያደረጋቸው ማህበረሰብ ነው ጥፋተኛው። ስለዚህ ድሆችን ለመደጎም፣ በእያንዳንዱ ሰራተኛና አምራች ላይ መንግስት እንዳሻው የታክስ ሸክም መከመር ይችላል” ማለታቸው ነው፡፡ “በራሴ ጥረት ያፈራሁት ምርትና ንብረት የኔ ነው፤ የራሴንና የቤተሰቤን ኑሮ ላሻሽልበት” ብሎ መከራከርም ሆነ አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ፣ አልያም በእምቢተኝነት መቃወም አይቻልም። ለምን?
አሃ፣ እንዲህ አይነት ክርክርና ተቃውሞ “ራስ ወዳድነት” ይሆናላ። ራስ ወዳድነት ደግሞ እንደሃጥያት ተቆጥሯል። እና ምን ትላላችሁ? አስታውሱ። “እያንዳንዱ ሰው ከየራሱ የግል ሃሳብና ጥቅም በፊት የሌሎችን ሃሳብና ጥቅም ማስቀደም አለበት። ከራስ ወዳድነት በመላቀቅ ራሱን ለሌሎች መስዋዕት ማድረግ ይገባዋል። የግል ማንነትንና ሰብእናን በማዋረድ፣ ለሌሎች መስገድና መገዛት ይኖርበታል” የሚሉ መፈክሮችን አትርሷቸው። መፈክሮቹን አሜን ብሎ የሚቀበል ሰው፣ አእምሮውንና የማሰብ ነፃነቱን፣ የስራ ፍሬውንና ንብረቱን፣ የግል ማንነቱንና የእኔነት ክብሩን ለማንም መንገደኛ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ይሆናል።
ራሱን ከበግ አሳንሶ ለመስዋዕትነት የተዘጋጀ ሰው ካለ ደግሞ፣ ሰውን ወደ መስዋዕት ቦታ ለመንዳት የሚቋምጡ ሶሻሊስቶች ይመቻቸዋል። ለዚህም ነው፤ የሶሻሊዝም ፖለቲካ በገነነ ቁጥር፣ በሃሳብ ነፃነት ፋንታ አፈናና ፕሮፓጋንዳ፣ በንብረት ባለቤትነት መብት ፋንታ የንብረት ውርስና የድህነት ራሽን፣ ከእኔነት ክብር ይልቅ ፍርሃትና ውርደት የሚስፋፋው። ለማንኛውም፤ የእንግሊዝ ሶሻሊስት ፓርቲዎች፣ እንደ ግሪክ አቻዎቻቸው ስልጣን እስከመያዝ ባይደርሱም፣ አምስት በመቶ ያህል ድጋፍ ለማሰባሰብ ችለዋል። ይህም ብቻ አይደለም።
አእምሮን የጠሉ የጭፍንነትና የሞት አምላኪዎች
አዎ፤ የባሰባቸው መጥተዋል። በአልቃይዳ ወይም በአይሲስ ቅኝት፤ “የምርጫ ፖለቲካን ከምድረ ገፅ እናጠፋለን” የሚሉ የሃይማኖት አክራሪዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። እነዚህም እንዲሁ፣ በግል ነፃነት ላይ የተመሰረተውን የካፒታሊዝም ስርዓት አይፈልጉትም። ስህተታቸውን፣ ጥፋታቸውንና እኩይነታቸውን እየተነተነ የሚሞግታቸው ቢመጣስ? ከጭፍንነት ተላቅቀው አእምሯቸውን ለመጠቀም ባይፈቅዱ እንኳ የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት ማክበር እንዳለባቸው የሚነግራቸውና “ነፃነቴ ይከበር” ብሎ የሚከራከር ቢያጋጥማቸውስ? እስካሁን ብርቱ ተከራካሪ ያጋጠማቸው አይመስልም። አልያም፣ ቀላል የማሸነፊያ ዘዴ ታጥቀዋል ማለት ነው። “ከግል አእምሮ በፊት የሃይማኖት እምነትን አስቀድም። ከግል ምድራዊ ሃሳብህና ጥቅምህ በፊት፣ የሃይማኖት ትዕዛዛትን አስቀድም” በማለት ማንኛውንም ተከራካሪ አፉን እንዲዘጋ ማድረግ እንደሚችሉ ያምናሉ።
“የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት አክብሩ በሚል የሚያዘጋጅም ሆነ ሌላ ምድራዊ ሕግ ማክበር የለብንም፤ በፈጣሪ ለተሰየመ መሪ ተገዢ መሆን አለብን” ከሚል ስብከት ጎን ለጎን፣ ራሳቸውን የፈጣሪ ተወካይ አድርገው በመሾም በሰው ሕይወት ላይ ይጫወታሉ። በእርግጥም፤ ዓለማዊነትን እያጥላላ፤ ማለትም የዚህ ምድር አእምሮውን፣ ሕይወቱንና ማንነቱን እያንቋሸሸ፣ “ከሞት ወዲያ”ን የሚናፍቅ ጭፍን የሞት አምላኪ፣ የሌሎች ሰዎችን ሕይወት ለማጥፋት ይሯሯጣል።  በደርዘን የሚቆጠሩ አገራትን በደም ጎርፍ እያጨቀዩ ያሉት እነዚሁ የሃይማኖት አክራሪዎች፣ በእንግሊዝና በሌሎች የአውሮፓ አገራት ውስጥ እየተበራከቱ መምጣታቸው ሚስጥር አይደለም።
የክርስትና ሃይማኖት አክራሪነት በሰፈነበት የጨለማ ዘመን፣ በምድረ አውሮፓ በርካታ ጳጳሳት በአገር ገዢነት እየነገሱና የለየላቸው ሃይማኖታዊ መንግስታት እየተመሰረቱ፣ ስንት እልቂትና ስቃይ እንደደረሰ መለስ ብሎ የሚመለከት ሰው የጠፋ ይመስል፤ ዛሬ በእስልምና አክራሪነት ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት ዘመቻ የሚያካሂዱ ነውጠኞችና አሸባሪዎች መግነናቸው ያሳዝናል። ይሄውና፤ በእንግሊዝና በሌሎች የአውሮፓ አገራት ዜግነት ያገኙ በሺ የሚቆጠሩ የመካከለኛው ምስራቅ ተወላጆች ወደ ኢራቅና ሶሪያ እየሄዱ፣ “እስላማዊ መንግስት (አይኤስ)” በሚል ስያሜ በሚታወቀው የሃይማኖት አክራሪዎች ቡድን ስር ተጠርንፈው እየተዋጉ ነው። ከአንድ ሺ የሚበልጡት ተዋጊዎች ከፈረንሳይ የሄዱ ናቸው። ወደ ፈረንሳይ እናምራ መሰለኝ።
የእንግሊዝን ፖለቲካ እየተፈታተኑ ያሉትን ሦስት የቀውስ ምንጮች አይተን የለ? ወደ ፈረንሳይ አቅጣጫ ስንዞርም፣ የተለየ ነገር አናገኝም። እነዚያው ሦስት ቀውሶች የአገሪቱን ፖለቲካ ሲያመሳቅሉ ነው የምንመለከተው። የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር በራሳቸው አንደበት የተናገሩትን መጥቀስ ይቻላል። ከስፔናዊ አባትና ከስዊዘርላንዳዊ እናት የተወለዱት የፈረንሳይ ጠ/ሚ ማኑኤል ቫልስ፣ በቅርቡ ለዎልስትሪት ጆርናል በሰጡት ቃለምልልስ የአገራቸው ዋና ዋና ፈተናዎችን ዘርዝረዋል። ቃለምልልሱ የጋዜጣውን ሰፊ ገፅ ከላይ እስከ ታች የሚሸፍን ረዥም ንግግር ቢሆንም፣ በሶስት ነጥቦች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው።
አንደኛ፣ የሃይማኖት አክራሪነት... ሁለተኛ፣ ዘረኝነት (ብሔረተኝነት)... ሦስተኛ፣ ወደ ሶሻሊዝም ያጋደለ ኢኮኖሚ። ጠ/ሚ ቫልስ ሌላ ጉዳይ አልቀላቀሉም - የፈረንሳይን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ህልውና የሚፈታተኑ ሦስት በሽታዎች ብቻ።
እንግዲህ አስቡት፡፡ “በዝቅተኛ ገቢ የሚኖር ብዙሃኑን ሕዝብ ለመደገፍና ለመደጎም” በሚለው የሶሻሊዝም ቅኝት፣ የፈረንሳይ መንግስት በተለያዩ ታክሶች አማካኝነት ከዜጎች ገቢ ውስጥ 57 በመቶ ያህሉን ይወስዳል።  የመንግስት እጅ ውስጥ የገባ ገንዘብ፣ ከፊሉ ለሙስና እየተጋለጠ፣ ገሚሱ በዝርክርክነት እየባከነ ኢኮኖሚን ይጎዳል። ከፊሉ ደግሞ በድጎማ እየተከፋፈለ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች፣ ለአጭር ጊዜ ሳይሆን ለዘለቄታው የመንግስት ጥገኛና የድጎማ ተመፅዋች እንዲሆኑ ያደፋፍራል። በአንድ በኩል፣ አምራችና ሃብት ፈጣሪ ሰዎች በታክስ ጫና እየተዳከሙና ከአገር እየለቀቁ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ይዳከማል፤ የስራ እድል ይቀንሳል፤ ስራ አጥነት ይባባሳል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በየጊዜው ከሚጨምረው የተደጓሚ ሰዎች ቁጥር ጋር፤ ከስራ ርቆ የመንግስትን ድጎማ የሚጠብቅ ስራ ፈት ይበራከታል።
ጠ/ሚ ቫልስ በራሳቸው ፓርቲ አማካኝነት እየተባባሰ የመጣውን ይህን ፈተና አድበስብሰው ለማለፍ አልሞከሩም። “ስራ ፈትነትን ስፖንሰር የምናደርግ መንግስት ሆነናል” በማለት ተናግረዋል ጠ/ሚ ቫልስ። በሌላ አነጋገር፣ “የሶሻሊዝም ዝንባሌ ከልክ አለፈ” እንደማለት ነው። እንዲህም ሆኖ፣ ሰውዬውና ፓርቲያቸው የካፒታሊዝም አቀንቃኝ ለመሆን ፈልገዋል ማለት አይደለም። ስልጣን ላይ የሚፈራረቁት ሁለቱ የፈረንሳይ ትልልቅ ፓርቲዎች፣ ራሳቸውን እንደለዘብተኛ ነው የሚቆጥሩት። ማለትም የቅይጥ ኢኮኖሚ አጋፋሪ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል፣ ከካፒታሊዝም ይልቅ ሶሻሊዝምን ያከብራሉ። ግን፤ የሰውን ንብረት በሚወርስ የሶሻሊዝም መንገድ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲንኮታኮት አይፈልጉም። ስለዚህ ምን ያድርጉ?
ሃብትን ለመፍጠር እድል የሚከፍት የካፒታሊዝም አሰራርን በከፊል፣ ከተፈጠረው ሃብት ውስጥ ገሚሱን መንግስት እንዲወስድ የሚያደርግ የሶሻሊዝም አሰራርንም በከፊል ተግባራዊ ማድረግን ይመርጣሉ - ለዘብተኞቹ ፓርቲዎች። እውነትም፣ የቅይጥ ኢኮኖሚ ተከታዮች ናቸው ማለት ይቻላል። ግን ቅጥይ ኢኮኖሚ አላዋጣም። አሁን ፈተና የሆነባቸው፣ የሶሻሊዝሙ ዝንባሌ እየበዛና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለጠጠ፣ ማቆሚያ የሌለው የቁልቁለት ጉዞ መምሰሉ ነው።
ከዘጠና አመት በፊት፣ መንግስት ከዜጎች ገቢ ውስጥ 8 በመቶ ገደማ ነበር የሚወስደው። የታክስ ጫናው፣ ቀስ በቀስ ወደ ሃያ እና ወደ ሰላሳ በመቶ እየጨመረ፣ ከዚያም ወደ አርባ እና ሃምሳ በመቶ እያለ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲብስበት እንጂ ሲሻሻል አይታይም። የታክስ ጫና የበዛባቸው አምራቾችና ሃብት ፈጣሪዎች፣ እንደምንም ተቃውሞ ለማሰማት ቢሞክሩ እንኳ ተደማጭነት አያገኙም። “ከግል ጥቅማችሁ በፊት የሌሎችን ጥቅምና የብዙሃኑን ፍላጎት አስቀድሙ” ብለው የሚደሰኩሩ ሶሻሊስቶች ናቸው የድጋፍ ጭብጨባ የሚጎርፍላቸው። አሁን፣ መንግስት ከዜጎቹ የስራ ገቢ ውስጥ 57% ያህል ይወስዳል።
አባትና ልጅን ያናከሰ ዘረኝነት
የፈረንሳይ በሽታ፣ ሶሻሊዝምና የሃይማኖት አክራሪነት ብቻ አይደለም። “ከግል ጥቅም በፊት የአገር ጥቅም ይቅደም” የሚል መፈክር የሚያስተጋባ ፒኤፍ የተሰኘ ብሔረተኛ ፓርቲ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገነነ መጥቷል። በአማካይ ከአምስት በመቶ በላይ የድጋፍ ድምፅ አግኝቶ የማያውቀው ፒኤፍ ፓርቲ፣ ባለፈው አመትና ዘንድሮ በተደረጉ የተለያዩ ምርጫዎች 25 በመቶ ገደማ ድጋፍ አግኝቷል። ነባሮቹ ትልልቅ ፓርቲዎች ከዚህ የበለጠ ውጤት አላስመዘገቡም።
ሰዎችን በግል ማንነታቸው (እንደየተግባራቸውና ባህርያቸው) ከመመዘን ይልቅ፣ የሰውን ማንነት በጅምላ እየፈረጀ በተወላጅነት  ለሟባደን የሚጥረው ይሄው ፓርቲ፣ “ነባር የፈረንሳይ ተወላጅ” እና “ከሌላ የአውሮፓ አገር ሰዎች የተወለደ መጤ” በማለት ይፈርጃል። የፒኤፍ ፓርቲ ፖለቲከኞች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ጭምር፣ “መጤ” በማለት ያንቋሽሻሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ “ነጭ” እና “ጥቁር” በሚል ለማቧደን ይቀሰቅሳሉ። አንዳንዴም፣ የአረብ ተወላጆች ላይ ወይም የቤተእስራኤል ተወላጆች ላይ የጥላቻ ጣታቸውን እየቀሰሩ ይዝታሉ። የአዶልፍ ሂትለር ናዚ ፓርቲ እንዳደረገው ነው፣ ሰዎች በተወላጅነት እየተቧደኑ በወዳጅነት መቀራረብና በጠላትነት መራራቅ ይኖርባቸዋል። ለምን? የሰው ማንነት የሚወሰነው በተወላጅነት ነው ብለው ያምናሉና። ከአርባ አመት በፊት፣ ለፔን የመሰረቱት የፈረንሳይ ብሔራዊ ግንባር (ፒኤፍ) የሚያራግበው መፈክርም ይሄው ነው።
ለበርካታ አመታት ፓርቲውን ሲመሩ የነበሩት ለፔን፣ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነው ሃላፊነቱን ለልጃቸው ሜሪን ለፔን ያስረከቡት። ሜሪን ለፔን ከአዛውንት አባቷ በተሻለ ሁኔታ የአባላት ምልመላ እና ቅስቀሳ በማካሄዷ፤ የፓርቲው ተቀባይነት እየጨመረ መጥቷል። አባቷ ግን ደስተኛ አልነበሩም። “ደጋፊ ለማብዛት ብለሽ የፓርቲውን አቋም አለሳልሰሻል” በማለት ቁጣቸውን በተደጋጋሚ ገልፀዋል። የተለሳለሰውን አቋም መልሶ ማጠናከር አለብኝ በሚል ስሜትም፣ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ተከታታይ ቃለምልልሶችን ሰጥተዋል - እንደወትሮው  የዘረኝነት ስሜትን የሚያግለበልቡ ያፈጠጡና ያገጠጡ ጭፍን ንግግሮችን በማራገብ።
በአባቷ ድርጊት የተናደደችው ሜሪን ለፔን፣ በተደጋጋሚ ልታስታግሳቸው ብትሞክርም አልተሳካላትም። በየመሃሉ፣ ለአፍታ እርቅ ያወረዱ ቢመስሉም፣ ብዙም ሳይቆይ እንደገና የሚያጣላ ነገር ይከሰታል። በአባቷ ሰፊ ሕንፃ ውስጥ ከፍቅረኛዋ ጋር ትኖር የነበረችው ሜሪን ለፔን፣ ንዴቷ ሞልቶ የፈሰሰው የዛሬ ወር ገደማ ነው። የሜሪን ለፔን ድመት ሞተች - የአባቷ ትልቅ ውሻ ነው ድመቷን የገደላት። ያኔ ሜሪን ህንፃውን ለቅቃ ወጣች። ባለፈው ሳምንት፣ አዛውንቱ ለፔን እንደገና ለአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ነውጠኛ ቃለምልልስ ለመስጠት ብቅ ሲሉ ግን፣ ሜሪን በጠሰች።
በቃ፤ አባቷ በፓርቲው የዲሲፕሊን ኮሚቴ ፊት ቀርበው ከፓርቲ አባልነት እንዲባረሩ ወሰነች። አባቷ ፓርቲውን እየጎዱ እንደሆነ የተናገረችው ሜሪን፣ “ይህንን የሚያደርገው፣ በክፋት ስሜት እየተገፋፋና በሕዝብ ዘንድ ስሙ የተዘነጋ ስለሚመስለው ዝናውን ለማስመለስ ነው” ብላለች። “በቃለምልልስ የሚናገራቸው ነገሮች ራሱንም ሆነ ፓርቲውን የሚጎዱ ናቸው። አገር ምድሩን ካላቃጠልኩ ሞቼ እገኛለሁ የሚል የአጥፍቶ ጠፊ መንፈስ ተጠናውቶታል። ከፓርቲ መሪነት ከወረደ በኋላ ፓርቲያችን በፍጥነት እያደገ ነው። ይሄም በቅናት ስሜት ያሳርረዋል” በማለትም አባቷን አውግዛለች።
ከፓርቲ አባልነት ከተባረሩ በኋላ፣ “እዚህ ያደረስኳት እኔ እንደሆንኩ ዘንግታለች” በማለት ቁጣቸውን የገለፁት ለፔን፣ “ከሁሉም የባሰች ጠላቴ እሷ ነች። ተቃናቃኝ ፓርቲዎች እንኳ ፊት ለፊት ነው ጥቃት ሲሰነዝሩብኝ የነበረው። ይህች ግን፣ ከጀርባ አድብታ ወጋችኝ” ብለዋል።
“በሚቀጥለው አመት በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ልጅዎ እንድታሸንፍ ይመኛሉ?” ተብለው የተጠየቁት ለፔን፤ “እንደሷ አይነት ቅሌታም ተመረጠ ማለት፣ የአገር ውርደት ነው።
ደግሞም ካላስገደለችኝ በቀር፣ ፈፅሞ ሰላም እንደማልሰጣትና እንደማልተኛላት ማወቅ አለባት። የሆነ ቦታ ሬሳዬ ከተገኘ ራሴን ያጠፋሁ እንዳይመስላችሁ” በማለት ልጃቸውን በደመኛ ጠላትነት ፈርጀዋል።
ሰኞ እለት ገንፍሎ በአደባባይ የፈነዳው የአባትና የልጅ እንካሰላንቲያ፣ ገና አልተቋጨም። በጋዜጣና በኢንተርኔት፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተጋጋለው የነቆራ ጦርነት፤ በፍርድ ቤት ወደ መካሰስ ያመራል ተብሏል። አንዳቸው አንዳቸውን ሳያደባዩ እንቅልፍ የሚወስዳቸው አይመስሉም።
በዚያ ሁሉ እንካሰላንቲያ መሃል ትንሽ ለማሰብ ቢሞክሩ’ኮ፣ አንዳች የሚያስማማ እውነተኛ ነገር ማግኘት ይችሉ ነበር። ግን ፈቃደኞች አይመስሉም። “ለካ፣ የፓርቲያችን ዘረኛ አቋም የተሳሳተ ነው። ለካ ወዳጅነትና ጠላትነት... በተወላጅነት የሚመጣ አይደለም። ለካ በዘር መቧደን ከንቱ ነው” የሚል እውነት ብልጭ አላለላቸውም። እናም፣ በጋራም ይሁን በተናጠል የፈረንሳይን ፖለቲካ ለማመሳቀል መቀስቀሳቸውን አያቋርጡም።  በስልጣኔ ደህና የተራመዱት የአውሮፓ አገራት፣ በሦስቱ የስልጣኔ ጠላቶች (ማለትም በሾሻሊዝም፣ በሃይማኖት አክራሪነትና በብሔረተኝነት) እየተናጡ የሚቃወሱ ከሆነ፤ ሌሎቻችን ምን ይውጠናል? እንደምታዩት ነባሩ የለዘብተኛነትና የቅይጥ አስተሳሰብ አቅጣጫ አውሮፓን ለቀውስና ለበሽታ የሚያጋልጥ እንጂ ስልጣኔን ከአደጋ ለመከላከል የሚያስችል አልሆነም። አንደኛ፤ ለአእምሮ፣ ለሳይንስና ለግል ነፃነት፣ ሁለተኛ፤ ለምርታማነት፣ ለግል ንብረትና ለብልጽግና፣…ሦስተኛ፤ ለግል ማንነት፤ ለእኔነት ክብር፣ ለራስ ወዳድነት ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ጽኑ የካፒታሊዝም አፍቃሪ የተመናመነባት ዘመን ነው፡፡ እናም ዘመኑ ለአውሮፓም ጭምር የሚያሰጋ የቀውስ ዘመን ቢሆን አይገርምም፡፡
ከአውሮፓ ውጭስ? ያማ እያየነው ነው፡፡ ብዙዎቹ የአረብና የአፍሪካ አገራት ከቀውስ አልፈው፣ በእርስበርስ እልቂት እየተተረማመሱ ነው - በሦስቱ የስልጣኔ ጠላቶች አማካኝነት፡፡  



Published in ከአለም ዙሪያ

የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ የአገሪቱ ህገ-መንግስት ከሚፈቅደው ውጭ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው ህገወጥነት እንደሆነና ውሳኔውን አጥብቆ እንደሚቃወመው የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በአገሪቱ የቀሰቀሰው ህዝባዊ ቁጣ እየተባባሰ መምጣቱ፣ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ አመቺ አይደለም ያለው የአፍሪካ ህብረት፣ የምርጫ ታዛቢ ቡድኑን ወደ አገሪቱ እንደማይልክም አስታውቋል፡፡ከስልጣናቸው እንዲወርዱ በአሜሪካ እየተደረገባቸው ያለውን ጫና የተቃወሙት ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በበኩላቸው፤ ቀጣዩ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ መከናወን እንዲችል ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያቆም ጥሪ አቅርበው፣ ለአራተኛ ዙር አገሪቱን ለመምራት እንደማይፈልጉና ከዚህ በኋላ በምርጫ እንደማይወዳደሩ ቃል ገብተዋል፡፡
ፖሊስ የአገሪቱን ዜጎች ደህንነት ለመጠበቅ ሲል በተቃውሞው የተሳተፉትን ሰዎች በማሰር ላይ እንደሚገኝና፣ ዜጎች ከመሰል ድርጊታቸው የሚታቀቡና ተቃውሞው የሚቆም ከሆነ የአገሪቱ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ዜጎች በሙሉ እንደሚፈቱም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡በብሩንዲ ያለው ሁኔታ አደገኛ ነው፡፡ ምርጫውን ለመታዘብ አንችልም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለሶስተኛ ዙር መወዳደራቸውም አግባብነት የለውም፤ የአገሪቱ ህገመንግስት ሊከበር ይገባል ብለዋል የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ንኮዛና ድላሚኒ ዙማ፤ ከቻይናው ሲሲቲቪ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ከትናንት በስቲያ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፡፡አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው ሲኤንዲዲ-ኤፍዲዲ ፓርቲ ከሁለት ሳምንታት በፊት የወቅቱን የአገሪቱ ፕሬዚደንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በመጪው ምርጫ በዕጩነት ማቅረቡን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከ15 ሰዎች በላይ መሞታቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ተቃውሞው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁሟል፡፡ሮይተርስ በበኩሉ፤ ከትናንት በስቲያ በአገሪቱ መዲና ቡጁምቡራ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎች የገዢው ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ አባል ነው ያሉትን አንድ ግለሰብ በእሳት አቃጥለው መግደላቸውንና የተለያዩ ሱቆችን ማጋየታቸውን ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለሶስተኛ ዙር ምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው የህግ ጥሰት ነው ያሉት የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ የአገሪቱ ህገመንግስት አንድ ፕሬዚዳንት በመሪነት መቆየት የሚችለው ለሁለት ዙር ብቻ እንደሆነ ቢወስንም፣ ፕሬዚዳንቱ ግን ህገመንግስቱን በጣሰ ሁኔታ በስልጣን ላይ ለመቆየት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱን የምርጫ ተሳትፎ አግባብነት በተመለከተ ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የብሩንዲ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት በበኩሉ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው ውሳኔው፣ ፕሬዚዳንቱ የመጀመሪያውን ዙር በፓርላማ እንጂ ቀጥታ በህዝቡ ተመርጠው ስልጣን ባለመያዛቸው እንደ አንድ ዙር አይቆጠርባቸውም፣ በዘንድሮው ምርጫ መወዳደር ይችላሉ ብሏል፡፡
የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳላይሬ ኒምፓጋሪትሴ ግን፣ ከመንግስት በተደረገ ጫና የተላለፈ ውሳኔ ነው በሚል ተቃውመው፣ ፊርማዬን አላስቀምጥም በማለት አገር ጥለው የተሰደዱ ሲሆን የአገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ በበኩሉ፤ ግለሰቡ ውሳኔውን እንዲያስተላልፉ ምንም አይነት ጫና እንዳልተደረገባቸው መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ለአመታት የዘለቀው ከ300 ሺህ በላይ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገው የአገሪቱ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት እ.ኤ.አ በ2005 ከተቋጨ ወዲህ አስከፊው የተባለውንና ከሰሞኑ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና አመጽ ተከትሎ፣ በአገሪቱ ውጥረት መንገሱንና 40 ሺህ የሚደርሱ የአገሪቱ ዜጎች ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ መሰደዳቸውንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ኦዲፋክስ ንዳቢቶሪየ የተባሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ባለፈው ረቡዕ  አመጹን አነሳስተዋል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ መለቀቃቸውን እንዲሁም በአገሪቱ መዲና ቡጁምቡራ ከትናንት በስቲያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አንድን ግለሰብ ተኩሶ መግደሉንና ሶስት ዜጎችንም ማቁሰሉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

መስራቾቹ ትርፋማ እንደሚሆኑ እርግጠኛ ሆነዋል
ሶስቱ ሰራተኞች በሶስት ሽፍት ይሰራሉ
ታላላቅ ኩባንያዎች ምርቶቹን ለመግዛት ተመዝግበዋል


ክላውድ ዲዲኤም የተባለውና በባለሶስት አውታር ህትመት ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ለመስራት ዝግጅቱን ያጠናቀቀው  የአሜሪካ ኩባንያ፣ በ3 ሰራተኞች ብቻ በሚያከናውነው የምርት እንቅስቃሴ ትርፋማ ስራ እንደሚያከናውን መስራቾቹ በእርግጠኝነት መናገራቸውን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነውና ሙሉ ለሙሉ በማሽን አማካይነት የሚሰራው ይህ ኩባንያ፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት በሆኑ 100 ባለ ሶስት አውታር ማተሚያ ማሽኖቹ አማካይነት በሳምንት ለ 7 ቀናት ለ24 ሰዓት የማምረት ስራውን የሚያከናውን ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው በሶስት ሽፍት ለ8 ሰዓታት የሚሰሩ 3 ሰራተኞች ብቻ እንዳሉትም ገልጽዋል፡፡
ከኩባንያው መስራች አንዱ የሆኑት ሚች ፍሪ ባለፈው ረቡዕ ለሲኤንኤን እንደገለጹት፣ ኩባንያው የምርት ስራውን በማተሚያ ማሽኖቹና በሶስቱ ሰራተኞች አማካይነት በተቀላጠፈ ሁኔታ እያከናወነ ሲሆን፣ ምርቶቹን የማሸግና ለደንበኞች የማድረስ ስራውን ደግሞ ዩፒኤስ የተባለ አጋር ድርጅት እያከናወነው ይገኛል፡፡
ኩባንያው የተለያዩ ቁሳቁሶችን በባለ ሶስት አውታር ማተሚያ ማሽኖች አማካይነት በማምረት ለደንበኞቹ የሚያቀርብ ሲሆን አሰራሩ የተቀላጠፈ በመሆኑ ለማምረት አንድ ሳምንት ያህል ጊዜ የሚወስዱ ዕቃዎችን በ24 ሰዓታት ውስጥ ሰርቶ ማጠናቀቅ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሚች ፍሪ ገልጸዋል፡፡
ኩባንያውን ለማቋቋም 1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉንና በቀጣይም የባለ ሶስት አውታር ማተሚያ ማሽኖቹን ቁጥር ወደ አንድ ሺህ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
ተቀማጭነቱ በኒውዮርክ የሆነው ሁማንስኬል የተባለ የቤት ዕቃዎች አምራች ኩባንያ፣ ታዋቂው የቅንጦት የእጅ ሰዓቶች አምራች ኩባንያ ዴቮን ዎርክስ እንዲሁም ግዙፉ ፍሌክስትሮኒክስን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች ከዚህ በአይነቱ የተለየ ኩባንያ ምርቶችን ለመግዛት ደንበኝነት መመስረታቸውንም አስታውቋል።

Published in ከአለም ዙሪያ

በአንድ የውድድር ዘመን ገቢና ትርፍ
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ - 4.5 ቢሊዮን ዶላር፤  137 ሚሊዮን ዶላር
የጀርመን ቦንደስ ሊጋ - 2.85 ቢሊዮን ዶላር ፤ 379 ሚሊዮን ዶላር
የስፔን ላ ሊጋ - 2.40 ቢሊዮን ዶላር ፤ 105 ሚሊዮን ዶላር
የጣሊያን ሴሪኤ - 2.17 ቢሊዮን ዶላር ፤  146 ሚሊዮን ዶላር
የፈረንሳይ ሊግ 1 - 1.80 ቢሊዮን ዶላር ፤ 85 ሚሊዮን ዶላር

በአንድ ጨዋታ የስታድዬም ተመልካች ብዛት በአማካይ
የጀርመን ቦንደስሊጋ - 42.6 ሺ
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ - 37.66ሺ
የስፔን ላሊጋ - 28.25ሺ
የጣሊያን ሴሪኤ - 23.3ሺ
የፈረንሳይ ሊግ 1 - 19.24 ሺ

በዓመታዊ የቴሌቭዥን ብሮድካስት ገቢ
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ - 3.39 ቢሊዮን ዶላር
የጣሊያን ሴሪኤ - 814.73 ሚሊዮን ዶላር
የፈረንሳይ ሊግ 1 - 656.53
የስፔን ላሊጋ - 577.43
የጀርመን ቦንደስ ሊጋ - 472.24

ዓመታዊ የማልያ ስፖንሰርሺፕ ገቢ
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ - 240.69 ሚሊዮን ዶላር
የጀርመን ቦንደስ ሊጋ - 157.07
የስፔን ላሊጋ - 127.69
የፈረንሳይ ሊግ 1 - 108.48
የጣሊያን ሴሪኤ - 94.92


የአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች በ2014/15 የውድድር ዘመን የመጨረሻ ወር ላይ ይገኛሉ፡፡ በሶስቱ ሊጎች ሻምፒዮኖቹ ክለቦች ታውቀዋል፡፡ ባየር ሙኒክ የጀርመን ቦንደስ ሊጋን ፤ ቼልሲ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን እንዲሁም  ጁቬንትስ የጣሊያን ሴሪኤን በማሸነፍ ሊጎቹ ከመጠናቀቃቸው 1 ወር በፊት  ሻምፒዮንነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የፈረንሳይ ሊግ 1 የሻምፒዮናነት ፉክክር ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች በፓሪስ ሴንትዠርመን እና በሊዮን መካከል የነበረውን የሻምፒዮናነት ትንቅንቅ ሊወሰን መቻሉ ተጠብቋል፡፡ በሌላ በኩል  በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ በቴሌቭዥን ስርጭት መብት በሚኖር የገቢ ክፍፍፍል በተፈጠረ ውዝግብ ከሳምንት በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ በፌደሬሽን ውሳኔ መተላለፉ ያልተጠበቀ ዜና ሆኗል፡፡ ከአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ሶስቱ ሻምፒዮን ክለቦቻቸውን ማወቃቸው እንዳለ ሆኖ ግን በየሊጎቹ በቀጣይ ውድድር ዘመን  ወደ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣርያ ቀጥታ ተሳትፎ ለማግኘት እና ከመውረድ ለመዳን የመጨረሻዎቹ  ሳምንታት ግጥሚያዎች  በወሳኝነታቸው  ትኩረት ስበዋል፡፡  
ከአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች በውድድር ዘመኑ በተመዘገበ ውጤት በወጣ የክለቦች ደረጃ ሪያል ማድሪድ 143.33 ነጥብ 1ኛ ደረጃ ይዟል፡፡ ሌላው የስፔን ክለብ ባርሴሎና 131.33 ነጥብ  2ኛ ሲሆን የጀርመኑ ሻምፒዮን ባየር ሙኒክ በ128.09 3ኛ፤ የእንግሊዙ ሻምፒዮን ቼልሲ በ122.72 ነጥብ  4ኛ  እንዲሁም ከ100 ነጥብ በታች በማስመዝገብ ከ10ኛ በታች የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንትዠርመን በ13ኛ እና የጣሊያኑ ጁቬንትስ  በ20ኛ ደረጃ  ተቀምጠዋል፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በሚወጣው በዚህ የውጤት ደረጃ መሰረት ከአንድ እስከ 20 ካሉት 25 በመቶው የእንግሊዝ፤ 20 በመቶው የስፔን ፤ 15 በመቶው የጀርመን፤ 10 በመቶው የፈረንሳይ እንዲሁም 5 በመቶው የጣሊያን ክለቦች መሆናቸውም ታውቋል፡፡
ከአምስቱ ታላላቅ ሊጎች ባሻገር በውድድር ዘመኑ ከፍተኛ ትኩረት ስቦ የቆየው እና ለ59ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚደረገው ፍልሚያ ባለፈው ሰሞን በግማሽ ፍፃሜ የመጀመርያ ጨዋታዎች ቀጥሏል። በዚህ መሰረት ጁቬንትስ በሜዳው ሪያል ማድሪድን 2ለ1 ያሸነፈ ሲሆን፤ ባርሴሎና ደግሞ በሜዳው ባየር ሙኒክን አስተናግዶ 3ለ0 በማሸነፍ የፍፃሜ ጉዟቸውን ተያይዘዋል፡፡ 59ኛውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ የምታስተናግደው የጀርመኗ በርሊን ከተማ ስትሆን በዋንጫ ጨዋታው ከ39 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚኖራት ተዘግቧል፡፡ በበርሊን ከተማ የሚገኘው ኦሎምፒያ ስታድዬን የዋንጫ ጨዋታው የሚካሄድበት ሲሆን ስታድዬሙ በ2006 እኤአ ላይ በጣሊያን እና በፈረንሳይ መካከል የተደረገውን የዋንጫ ጨዋታ አስተናግዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የዘንድሮ ውድድሮች የጣሊያን ክለቦች ስኬታማ መሆናቸው ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚጠቀስ ይሆናል፡፡ ስለሆነም የጣሊያን ክለቦች በሁለቱ የአውሮፓ ታላላቅ ውድድሮች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ዩሮፓ ሊግ ያስመዘገቡት ስኬት በተለይ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ያላቸውን ኮታ ከ3 ወደ አራት ለማብዛት የሚያግዛቸው ይሆናል፡፡ አራተኛውን ኮታ የሚነጥቁት ደግሞ ደካማ ተሳትፎ የነበራቸውን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦችን በመተካት ነው፡፡ ከሶስት የውድድር ዘመናት በፊት የጣሊያን ክለቦች አራት ክለቦች በቀጥታ ወደ የምድብ ማጣርያ የማስገባት እድላቸው በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ክለቦች ተነጥቆ ነበር፡፡ በዘንድሮው የአውሮፓ ውድድሮች ላይ የእንግሊዝ ክለቦች ከሩብ ፍፃሜ ባለማለፋቸው እና የጣሊያን ክለቦች ደግሞ ጁቬንትስ በሻምፒዮንስ ሊግ እንዲሁም ናፖሊ እና ፊዮረንቲና በዩሮፓ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ በመግባት ስኬታማ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በተያያዘ የአውሮፓ ክለቦች በቴሌቭዥ ስርጭት መብት እና በስፖንሰርሺፕ ውሎች በየዓመቱ ገቢያቸው እና ሃብታቸው እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው ሲል ሰሞኑን የወጣው የፎርብስ መፅሄት ጥናታዊ መረጃ ያመለክታል፡፡ በዓለም እግር ኳስ ከፍተኛ ዋጋ  ያላቸው 20 ክለቦች በአማካይ 1.16 ቢሊዮን ዶላር ተመን እንዳላቸው የሚያወሳው ፎርብስ ይህ ተመን ካላፈው የውድድር ዘመን በ11 በመቶ እድገት እንዳሳየ እና ከአምስት አመት በፊት ከነበረው በ84 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ይገልፃል። ከዓለማችን ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው 20 ክለቦች መካከል ደግሞ በተለይ 6 ክለቦች ሪያል ማድሪድ፤ ባርሴሎና፤ ቼልሲ፤ ሊቨርፑል፤ ማንችስተር ሲ እና ማንችስተር ዩናይትድ በኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆች ባላቸው ተከታታይ ብዛት፤ በጨዋታ ቀን ገቢ፤ በብሮድካስት ገቢ እንዲሁም በተለያዩ ንግዶች ገቢያቸው እስከ 10 ባለው ደረጃ በግንባር ቀደምነት በመካተት ተጠቃሽ ሆነዋል። በከፍተኛ ዋጋው የሚመራው በ3.26 ቢሊዮን ዶላር የተተመነው የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ሲሆን ዘንድሮ ብቻ ያስመዘገበው 746 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከየትኛውም የዓለም ስፖርት ቡድን በቀዳሚነት የሚያስቀምጠው ነው፡፡ ሪያል ማድሪድ በአንድ የውድድር ዘመን ያስመዘገበው ተንቀሳቃሽ ትርፍ 171 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በቸኛው የበሚበልጠው ክለቡ የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ ባስመዘገበው 173 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በከፍተኛ ዋጋው ሪያል ማድሪድን የሚከተለው ሌላው የስፔን ክለብ ባርሴሎና በ3.16 ቢሊዮን ዶላር ተመኑ ነው፡፡ የእግሊዙ ማንችስተር ዩናይትድ በ3.1 ቢሊዮን ዶላር ፤ የጀርመኑ ባየር ሙኒክ በ2.35 ቢሊዮን ዶላር፤ የእንግሊዞቹ ማንችስትር ሲቲ በ1.38 ቢሊዮን ዶላር፤ ቼልሲ በ1.37 ቢሊዮን ዶላር፤ አርሰናል በ1.31 ቢሊዮን ዶላር፤ ሊቨርፑል በ982 ሚሊዮን ዶላር፤ የጣሊያኖቹ ጁቬንትስ በ837 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ኤሲ ሚላን በ775 ሚሊዮን ዶላር የዋጋ ተመናቸው ከ4 እስከ 10 ያለውን ደረጃ አከታትለው ይወስዳሉ፡፡
በ23ኛው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ከሳምንት በፊት ባደረጋቸው 35ጨዋታዎች 83 ነጥብ እና 42 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ ማሸነፉን ያረጋገጠው የምእራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ነው፡፡ ሊጉ ከሶስት ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ የሚጠናቀቅ ቢሆንም በሽልማት ገንዘብና በተለያዩ የገቢ ድርሻዎች ተሳታፊ  ሃያ ክለቦች 1.7 ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚከፋፈሉ ታውቋል፡፡ ሻምፒዮኑ ቼልሲ 148.50 ሚሊዮን ዶላር ሲያገኝ፤ ማን. ዩናይትድ 148.35፤  አርሰናል 146.68፤ ማን ሲቲ 143.49 እንዲሁም ሊቨርፑል 140.14 ሚሊየን ዶላር ድርሻ አላቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሻምፒዮኑ ክለብ ቼልሲ በለውጥ ሁኔታዎች ውስጥ ይገኛል፡፡ ከሁለት የውድድር ዘመን በፊት በቼልሲ ክለብ እስከ 2017  እኤአ ለመቆየት ውል የፈፀሙት ጆሴ ሞውሪንሆ የሊጉ ሻምፒዮን ለመሆን ከቻሉ በኋላ ኮንትራታቸው በተጨማሪ ሁለት የውድድር ዘመናት እንዲራዘም በቼልሲ ደጋፊዎች ግፊት እየተደረገ ነው፡፡
ለዚህም የቼልሲ ክለብ ለጆሴ ሞውሪንሆ እስከ 2019 እኤአ ድረስ ለሚቀጥል ቆይታቸው አስቀድሞ ከነበራቸው ደሞዝ የ2.1 ሚሊዮን ፓውንድ ጭማሪ በማድረግ በየዓመቱ 10.5 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል እቅድ መኖሩ ተዘግቧል፡፡ በሌላ በኩል ቼልሲ ሁለተኛውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ድል በቀጣይ የውድድር ዘመን በጆሴ ሞውሪንሆ አሰልጣኝነት የሚያሳካ ከሆነ ለአሰልጣኙ የ5 ሚሊዮን ዶላር ቦነስ ለመስጠት ፍላጎት እንዳለም ተገልጿል፡፡
በፕሪሚዬር ሊጉ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የሚደረጉ ጨዋታዎች በሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣርያ በቀጥታ ለመግባት ከ2 እስከ 4 ደረጃ የሚደረጉ ትንቅንቆች ናቸው፡፡ ማን. ሲቲ በ35 ጨዋታዎች 70 ነጥብ እንዲሁም አርሰናል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ70 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስትኛ ደረጃ ላይ በመገኘት ከፍተኛው እድል ይዘዋል፡፡ ሊቨርፑል እና ማን. ዩናይትድ ደግሞ በሻምፒዮንስ ሊጉ የጥሎ ማለፍ ማጣርያ ለመግባት በሚያስችለው 4ኛ ደረጃ ለመጨረስ ከባድ ፍልሚያዎችን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡  በወራጅ ቀጠናው ያለው ትንቅንቅም ከፈትኛ ትኩረት ስቦ ይቀጥላል። አስቶን ቪላ፤ ኒውካስትል ዩናይትድ፤ ሌችስተር እና ሃልሲቲ አስተማማኝ በማይባሉ ደረጃዎች የሚገኙ ሲሆን ሰንደርላንድ፤ ኪውንስ ፓርክ ሬንጀርስ እና በርንሌይ በወራጅ አጣብቂኝ ሆነው ትግላቸውን ያደርጋሉ፡፡
በ52ኛው የጀርመን ቦንደስ ሊጋ
የቦንደስ ሊጋውን ሻምፒዮናነት ባየር ሙኒክ ያረጋገጠው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር፡፡ በ31 ጨዋታዎች 76 ነጥብ እና 62 የግብ ክፍያ ካስመዘገበ በኋላ ነው፡፡ ለባየር ሙኒክ በቦንደስ ሊጋው ባለፉት 15 ዓመታት ለ9ኛ ጊዜ ያሳካው የሻምፒዮናነት ክብር ነው። በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከባየር ሙኒክ በመቀጠል ለቀሩት የቀጣይ የውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣርያ ሁለት ኮታዎች ዎልፍስበርግ እና ባየር ሌቨርኩዘን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ ቀሪ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎቻቸውን በትኩረት ያደርጋሉ። በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦርስያ ሞንቼግላድባክ  በሻምፒዮንስ የጥሎ ማለፍ ማጣርያ ውስጥ ለመግባት በቅርብ ተቀናቃኝነት ዱካቸውን ተከትሎ ይገኛል። በወራጅ ቀጠናው በ3 ነጥብ ልዩነት ሁለት ክለቦች አንዳቸው ላለመውረድ ትንቅንቅ ውስጥ ናቸው፡፡ሃምበርግ ኤስቪ የመትረፍ እድል ይዟል፡፡  ስቱትጋርት እና ሃንሆቨር ግን መውረዳቸው አይቀርም፡፡
ባየር ሙኒክ ባለፉት አምስ የውድድር ዘመናት በቦንደስ ሊጋው ያገኘው ስኬት በከፍተኛ ገቢ ተጠቃሚ አድርጎታል፡፡ በአውሮፓ እና በጀርመን ውድድሮች ከፍተኛ ገቢ በማግኘቱ ክለቡ የሚጫወትበት ስታድዬም አሊያንዝ አሬናን ለመገንባት የገባበትን እዳ ገና 15 ዓመታት እየቀረው ከፍሎ ለመጨረስ በቅቷል፡፡ ይህን ስኬቱን ለመቀጠል በሚቀጥሉት የውድድር ዘመናት ክለቡን በፔፔ ጋርዲዮላ አሰልጣኝነት ለማስቀጠል ይፈልጋል፡፡ በ2016 እኤአ ላይ ኮንትራቱ የሚያልቀው ፔፔ ጋርዲዮላ ባለፈው የውድድር ዘመን የቦንደስ ሊጋ እና የጀርመን ካፕ ሁለት ዋንጫዎች እንዲሁም ዘንድሮ የቦንደስ ሊጋ ሻምፒዮናነት ክብርን አግኝቷል፡፡ ክለቡ አሰልጣኙን ለማስቀጠል ፍላጎት እንዳለው እየተገለፀም ነው፡፡ ማንችስተር ሲቲ ፔፔ ጋርዲዮላን ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ለማዛወር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በ80ኛው የጣሊያን ሴሪ ኤ
በሴሪኤው ለአራተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን ሻምፒዮንነቱን በማረጋገጥ የስኩዴቶውን ክብር የተቀዳጀው ጁቬንትስ ነው፡፡ ጁቬንቱስ በሴሪኤው በ34 ጨዋታዎች  74 ነጥብ እና  45 የግብ ክፍያ ካስመዘገበ በኋላ ማሸነፉን  አረጋግጧል፡፡ ጁቬንትስን ተከትለው በደረጃ ሰንጠረዡ ከ2 እስከ 4 ያለውን ደረጃ የያዙት ሮማ፤ ላዚዮ  እና ናፖሊ በቀጣይ የውድድር ዘመን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን የምድብ ማጣርያ ቀጥታ ተሳትፎ ለማግኘት ትንቅንቅ ውስጥ ናቸው፡፡ ከሶስቱ ክለቦች የተለየ የሻምፒዮንስ ሊግ የተሳትፎ እድል የያዘው በራፋኤል ቤኒቴዝ የሚሰለጥነው ናፖሊ ሲሆን በዩሮፓ ሊግ አሸናፊነት ስኬታማ ለመሆን ከቻለ ብቻ ይሆናል፡፡
በወራጅ ቀጠና ውስጥ እየዳከሩ ያሉት  ሴሴና እና ካግሊያሪ ናቸው፡፡ ፓርማ ወርዷል፡፡
ጁቬንትስ የሴሪኤውን የስኩዴቶ ክብር ዘንድሮ የተቀዳጀው ለአራተኛ የውድድር ዘመን በተከታታይ ነው፡፡ አስቀድሞ ሶስቱን የስኩዴቶ የሻምፒዮናነት ክብሮች አከታትሎ የወሰደው በቀድሞው አሰልጣኙ አንቶኒዮ ኮንቴ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ አራተኛውን ማክስ አሌግሪ አሳክተውታል፡፡ በጣሊያን ሴሪኤ የተሳትፎ ክብሩ 31ኛው የስኩዴቶ ድል ያገኘው ጁቬንትስ በ2004/05 እና በ2005/ 06 አከታትሎ ያገኛቸውን የስኩዴቶ ክብሮች በካልቺዮፖሊ ቅሌት መነጠቁ የማይዘነጋ ሲሆን ደጋፊዎቹ ግን እነዚህን የስኩዴቶ ክብሮች በመቁጠር ሴሪኤውን 33 ጊዜ አሸንፈናል በሚል ማስታወቂያቸውን በስታድዬም ይዘው በተደጋጋሚ ታይተዋል፡፡
በ77ኛው የፈረንሳይ ሊግ 1
የፈረንሳይ ሊግ 1 የሻምፒዮናነት ትንቅንቅ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታዎች ሊወሰን እንደሚችል ነው የተገመተው፡፡ ፓሪስ ሴንትዠርመንና እና ሊዮን ተናንቀውበታል፡፡ ሊግ 1 ከአምስቱ ሊጎች የላቀው ፉክክከር ዘንድሮ ታይቶበታል፡፡ ከ2 ሳምንት በፊት ኦለምፒክ ሊዮን የሊጉን ደረጃ ሰንጠረዥ  ፒኤስጂን በጎል ክፍያ ብልጫ በመውሰድ ይመራ ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ፒኤስጂ በ35 ጨዋታዎች 74 ነጥብ አስመዝግቦ ኦሎምፒክ ሊዮንን በ3 ነጥብ በመብለጥ ወደ ሻምፒዮንነቱ ክብር እየገሰገሰ ይገኛል፡፡  ከሁለቱ ክለቦች ሌላ ሞናኮ፤ ማርሴይ እና ቦርዶ በሶስተኛ ደረጃ በመጨረስ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ ለመብቃት በያዙት ትንቅንቅ የመጨረሻዎቹን ሳንምታት ይፋለማሉ፡፡
በወራጅ ቀጠናው ኤስያን እና ሜትዝ ለመዳን የማይችሉበትን ጠባብ እድል ይዘው እየታገሉ ሲሆን ሌንስ መውረዱ እርግጥ ሆኗል፡፡
ለ84ኛየስፔን ላሊጋ
በስፔን ላሊጋ ለሻምፒዮናነት ክብሩ በሁለት ነጥብ ልዩነት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ይዘው ያሉት ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ናቸው፡፡ ይ ባርሴሎና በ35 ጨዋታ 87 ነጥብ እና 86 የግብ ክፍያ ሲያስመዘግብ ሪያል ማድሪድ የሚከተለው በ85 ነጥብ እና በ73 የግብ ክፍያ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የስፔን እግር ኳስ ፌደሬሽን የላሊጋው የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታዎች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጡ መወሰኑን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ማስታወቁ የላሊጋውን ሂደት የሚያስተጓጉለው ይመስላል፡፡ ፌደሬሽኑ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በሊጉ የቴሌቭዥ ስርጭት መብት ገቢ ዙርያ ክለቦች እና መንግስት በገቡት ውዝግብ ሳቢያ ነው፡፡
ፌደሬሽኑ ከቲቪ ገቢ የሚያገኘው 4.45 በመቶ ድርሻ በቂ አይደለም በሚል ከመንግስት ጋር ላለፉት ሶስት ወራት ሲያደርግ የነበረው ድርድር ውጤታማ ባለመሆኑ የእግድ ውሳኔውን ለማስተላለፍ ግድ እንደሆነበት አስታውቋል፡፡ የእግድ ውሳኔው የላሊጋ ጨዋታዎችን ብቻ ሳይሆን፤ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እና ሌሎች በፌደሬሽኑ የሚደረጉ ውድድድሮችን የሚያካትት ሲሆን ከ600ሺ በላይ ተጨዋቾች የሚሳተፉባቸው 30ሺ ጨዋታዎችን የሚያግድ ነው ተብሏል፡፡
ውዝግቡ የሚቋጭ ከሆነ ሻምፒዮን ለመሆን ሰፊ እድል ያለው ባርሴሎና ነው፡፡ ሪያል ማድሪድ በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ በአትሌቲኮ ማድሪድ ሜዳ የሚኖረው ግጥሚያ የዋንጫ ፉክክሩን ያከብድበታል፡፡ አትሌቲኮ ማድሪድ በያዘው የሶስተኛነት ደረጃ ለቀጣይ የውድድር ዘመን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣርያ ቀጥታ ተሳትፎ ባለው እድል ይገኛል፡፡ ይሁንና ለቀሪው የሻምፒዮንስ ሊግ አራተኛ የተሳትፎ ኮታ ቫሌንሽያ የተሻለ እድል ቢኖረውም ሎስቼ እና ሲቪላ በቅርብ ርቀት ፉክክራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ከላሊጋው መውረዱ የተረጋገጠው ክለብ ኮርዶባ ሲሆን ግራናዳ፤ ኤይባር እና አልሜርያ የመዳን እድል ይዘው ይቀጥላሉ፡፡ ዴፖርቲቮ ላካሩኛ እና በዴቪድ ሞየስ የሚሰለጥነው ሪያል ሶሲየዳድ ግን አደጋው ውስጥ ናቸው፡፡

ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመፃሕፍት ንባብ እና ውይይት ፕሮግራም በነገው ዕለት “ዘ ማሳካር ኦፍ ደብረ ሊባኖስ ኢትዮጵያ 1937” በተሰኘው የደራሲ ኢያን ካምፔል መጽሐፍ ላይ በነገው ዕለት በብሔራዊ ቤተመፃሕፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ውይይት ያካሂዳል፡፡
ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምሕር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ሲሆኑ የሥነ ፅሁፍ ቤተሰቦች በዚህ ውይይት ላይ እንዲታደሙ ሚዩዚክ ሜይዴይ ጋብዟል፡፡
ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ለ6 ወራት ያህል በየ15 ቀኑ የሚያደርገውን የመፃህፍት ውይይት አቋርጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በስንዱ ቢሰነብት የተዘጋጀው “እንዳታነቡኝ” የተሰኘ የግጥም መድበልና የህይወት መዘክር የፊታችን ሰኞ በዋቢሸበሌ ሆቴል ይመረቃል፡፡ መፅሐፉ አንጋፋውን የኪነጥበብ ባለሙያ ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) የህይወት ታሪክና ተመክሮ እንዳካተተ ታውቋል፡፡ “እንዳታነቡኝ” በ25 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያን አየር ኃይል የ70 ዓመት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ዛሬ በካፒታል ሆቴል ከ4 ሰዓት ጀምሮ  ይመረቃል፡፡ መጽሐፉ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገራት የተሰባሰቡ የአየር ኃይልን መረጃዎች  የያዘ ሲሆን ለመጪው ትውልድ ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡  በ750 ገጾች የተቀነበበው መጽሃፉ፤ ዋጋው 350 ብር ሲሆን ከሰኞ ጀምሮ ገበያ ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡

ታዋቂው ደራሲና ጋዜጠኛ አብርሃም ረታ ዓለሙ በህይወት ሳለ የተረጐመው “አባቶችና ልጆች እና ሌሎች ታሪኮች” የተሰኘው መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ የበቃ ሲሆን የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ አዳራሽ ይመረቃል ተብሏል፡፡ መጽሐፉ 15 አጫጭር ታሪኮችን ያካተተ ሲሆን  በ49 ብር እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛ አብርሃም ረታ አለሙ በተለያዩ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ውስጥ በጋዜጠኛነት የሠራ ሲሆን በ1999 ዓ.ም የሩህ ጋዜጣ አዘጋጅ በነበረበት ወቅት በቀረበበት ክስ ተፈርዶበት ለአንድ ዓመት በእስር ቆይቷል፡፡ አብርሃም ግንቦት 11 ቀን 2000 ዓ.ም በድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል፡፡ ከመጽሐፍ ምረቃ ሥነስርዓቱ ጋር ሰባተኛ የሙት ዓመት መታሰቢያውም እንደሚከበር ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል፡፡  

    የሰው ልጅ በተለያዩ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ችግሮች ከሀገር ሀገር ሊሰደድ ይችላል፡፡ የስደት መልኩ ውብ ሆኖ አያውቅም፡፡ ስደት በችግር ጊዜ መልከመልካም መስሎ የሚታይ መልከ ጥፉ ነው፡፡ ስደትን የራሱ ባልሆነ ተክለ ቁመና ማራኪ ሆኖ እንዲታይ የሚያደርገው የችግራችን ስፋትና ጥልቀት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ከ1960ዎቹ በፊት ጐልቶ የሚታይ የስደት ታሪክ ያልነበራቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ ከ1960ዎቹ ወዲህ ግን የኢትዮጵያውያን ስደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የሀምሳዎቹና የስልሳዎቹ እንዲሁም ሰባዎቹ ስደት ምክንያት ፖለቲካ ነበር፡፡
አሁንም በፖለቲካው ምክንያት ለስደት የተዳረጉ ዜጐች ቢኖሩም፤ የአብዛኛው ስደተኛ የስደት ምክንያት ግን ኑሮ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያኑን ችግርና እጦት ለስደት ዳርጓቸዋል፡፡
በተስፋዬ ዘርፉ የተፃፈው “የስደታችን ትውስታ” የተሰኘው መጽሐፍ ስደትን የሚያስቃኝ፣ በ184 ገፆች የተቀነበበ መጠነኛ ታሪክ ነው፡፡ ደራሲው ተስፋዬ ዘርፉ እና ጓደኞቹ ለስደት የተዳረጉት በፖለቲካ አመለካከታቸውና አቋማቸው ምክንያት ነው፡፡ ዛሬም በፖለቲካ ምክንያት የሚሰደዱ ለመኖራቸው የዓይን እማኝ ነኝ፡፡ ነገር ግን አሁን ጐልቶና ገኖ የሚታየው የስደት ዓይነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ነው፡፡ ሰው በሀገሩ ላቡን እያንጠባጠበ አላልፍለት ሲለው፣ የሚበላውን አጥቶ በረሃብ አለንጋ ሲገረፍ፤ ሲራብ፣ ሲጠማ፣ ሲታረዝ፤ እስኪ እኔም ሂጄ የዕድሌን ልሞክር ብሎ ይሰደዳል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ አሳዛኝ እውነት!
አብዛኛው የዘመኑ ወጣት ቁጭ ብሎ በረሃብና በችግር ከመጠቃትና ቁጭ ብሎ ከመሞት፣ በተስፋ ልቡን አብርቶ ወደ ነገ እግሩን አንስቶ፣ እንቅስቃሴ ላይ እያለ መሞት የመረጠ ይመስላል፡፡ ተቀምጦ ከማሸለብ ቆሞ መሄድ፣ ተኝቶ ከመሞትም በርትቶ በመሰደድ ህይወቱን ለመለወጥ የወሰነ መሆኑን በየጊዜው የምናያቸው ሁኔታዎችና እውነታዎች ይመሰክራሉ፡፡ ምርጫው ከሁለት አንድ ነው፡፡ ሞት ወይ ሽረት!
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ ከመጽሐፍ ጀርባ ላይ የሰፈሩትን አስተያየት፤ ሁሉም ሰው ቢያነብ መልካም ነውና እዚህ እጠቅሰዋለሁ፡-
“ስደት የሰው ልጅ በማህበር መደራጀት ከጀመረበት ጀምሮ ያልተለየው ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ ምክንያቶቹ ተፈጥሯዊ ወይም ማህበረሰባዊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መጠኑ ሊበዛም ሊያንስም ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክም ይህንኑ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ገጽታ ከሞላ ጐደል ያንፀባርቃል፡፡ በተለይ የሃያኛው መቶ ዓመት አያሌ ኢትዮጵያዊያን በተለያየ ምክንያት ካገራቸው ለመሰደድ የተገደዱበት ዘመን ነበር፡፡”
የታሪክ ተመራማሪው ይህን ብቻ ብለው አያበቁም፤ ስለ መጽሐፉ በተለይ፤ ስለ ስደትም በአጠቃላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-
“አሁን ለህትመት የበቃው የተስፋዬ መጽሐፍ የዚህን ታሪክ አንድ ምዕራፍ ሥዕላዊ በሆነና ቀልብን በእጅጉ በሚስብ መንገድ ይተርካል፡፡ ወቅቱ የ1960ዎቹ ዓመታት የኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት፤ ከመንግሥት ጋር ያደርጉት የነበረው ፍልሚያ ጣራ የነካበት፤ በተለይ በታህሳሥ 1962 የተማሪዎች መሪ ጥላሁን ግዛው ከተገደለ በኋላ በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ተማሪዎች ከፀጥታ ኃይሎች ወከባ ለማምለጥ የነበራቸው ምርጫ ስደት ነበር፡፡”
የድሮውን ስደት ካሁኑ ስደት ጋር ስናወዳድረው፣ የአሁኑ እጅግ አሳዛኝና የከፋ ሆኖ ይታያል፡፡ የፖለቲካ ተጋድሎ ማድረግ ህልው ከመሆን ከፍ ብሎ የሚገኝ፣ እንደ ሰው አንድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረስ ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡
የሆድ ጥያቄ ቀላል አይደለም፡፡ አሁን ኢትዮጵያዊያን እየተሰደዱ ያሉት የሆድን ጥያቄ ለመመለስና ከድህነት ለማምለጥ ነው፡፡ ይህ ያፈጠጠ እውነት መሆኑ ቅስም ይሰብራል፣ ልብ ያደማል፣ ነፍስ ያቆስላል፡፡ ይህ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ያፈጠጠ እውነት በመሆኑ ልንክደውም ሆነ ልናመልጠው አይቻለንም፡፡ ያለን ብቸኛው ምርጫ እውነቱን ፊት ለፊት መጋፈጥ ነው፡፡
ደራሲው ተስፋዬ ዘርፉ ነገሌ ቦረና የተወለደና ያደገ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ነገሌ ቦረና እና ጅማ ከተማ ተከታትሎ፤ በበዕደማርያም የሚሰጠውን ትምህርት ቀስሞ፤ በ1960 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን መከታተል ችሎ እንደነበር ይገልፃል፡፡
በኃይለሥላሴ መንግስትና በተማሪዎች መሀል የተቃውሞና የእስር፤ የትችትና የሞት ክስተቶች ተከታትለው የተጓዙበት ነበር፤ ዘመኑ፡፡ ተስፋዬም ተማሪ በመሆኑ የመንግሥቱን ውድቀት የሚመኝ ተቃዋሚ ነበር፡፡ ምክንያቱም የዘመኑን ትኩሳት የሚጋራ ግለሰብ ነውና፡፡
የቀደመ ዘመን ስደትና የዚህ የኛ ዘመኑ ስደት ምክንያትና ውጤቱ የተለያየ ሊሲሆን ቢችልም፤ ሁለቱም ዘመኖች የሚጋሩት የራሳቸው የሆነ ተመሳሳይነት እንዳላቸው መረዳት ይቻላል፡፡ በቅርቡ በሊቢያ በምህረት የለሹ የአይኤስ ቡድን የታረዱት ሰላሳ ኢትዮጵያውያንና በርካታ ዜጐች በረሃ ለበረሃ እያቋረጡ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚያደርጉት የስቃይ ጉዞ፤ አጀማመሩ ከነተስፋዬ ስደት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፡፡
ተስፋዬ ለመሰደድ ከወሰነ በኋላ ያደረገውን የመጀመሪያ ዝግጅቱን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-
“…በተለያዩ አካባቢዎች ወደሚኖሩ ዘመዶቼ ዘንድ በመሄድ በዘዴ ገንዘብ ለማሰባሰብ ሞከርኩ። ያገኘሁት ግን በቂ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ለጉዞው ዝግጅት ያለኝ ጊዜ እያጠረ መሄዱን በመገንዘብ በሥራ ዓለም በነበርኩበት ጊዜ የገዛኋቸውን ዕቃዎች ከየነበሩበት ቦታ በማውጣት ጥቂት በቻ አስቀርቼ የነበሩኝን ልብሶች በሙሉ አሮጌ ተራ ወስጄ በተገኘው ዋጋ ሸጥኩ፡፡”
ይህ ከዛሬ አርባ አምስትና ሃምሳ ዓመት በፊት የተከወነ ነው፡፡ ነገር ግን በዛሬ የስደት ታሪካችን ውስጥም ጎልቶ የሚታይ ሃቅ ነው፡፡ ያላቸውን ንብረት ሸጠው ለህገወጥ ደላሎች ገንዘባቸውን የሚከሰክሱ ሞልተዋል፡፡ ለዚያውም በስንትና ስንት ልመናና ውጣ ውረድ በኋላ ያገኙትን ገንዘብ!
የራሳቸውን ንብረት ሸጠው፤ ከዚህም ከዚያም ተበድረውና ተለቅተው ብቻ ሳይሆን የገበሬ አባታቸውን በሬና መሬት፤ የእናታቸውን ወርቅና ጌጥ ሸጠው የሚሰደዱ ጥቂት አይደሉም፡፡ ጥቂት አይደሉም ሳይሆን ብዙ ናቸው፡፡
*   *   *
ለመሰደድ ቁርጥ ውሳኔ ላይ የደረሱት ተስፋዬና ሁለቱ ጓደኞቹ በምዕራብ ኢትዮጵያ በመንዲ በኩል አድርገው ወደ ሱዳን ለመሻገር አውቶብስ ተሳፍረው ከአዲስ አበባ ተነሱ፡፡ እዚያው መኪና ውስጥ የተዋወቋቸው መምህራን (በኋላ ነጋዴዎች መሆናቸውን ተረድተዋል)፤ ራሳቸው ዘንድ ሊያሳርፏቸው እንደሚችሉና ከመንዲ ወደፈለጉበት እንዲሄዱ መንገድ እንደሚያመቻቹላቸው ቃል ከገቡላቸው በኋላ ለመንገድ አመልካቾች በሚል ገንዘብ ተቀበሏቸው፡፡ እነ ተስፋዬ በተባሉት ሰዓት፤ የተባሉበት ቦታ ላይ ሆነው መንገድ መሪዎቹ ከአሁን አሁን መጡ ብለው በጉጉት ሲጠብቁ፤ በፖሊስ ተከበቡ፡፡
የኤርትራ ነፃ አውጪ ተዋጊዎች ከመሆናቸውም በላይ ብዙ መሳሪያና ቦምብ በአህያ ጭነው ወደ ሱዳን ለመሻገር የተሰናዱ ወንበዴዎች ናቸው፤ በሚል ክስ እዛው መንዲ ለአንድ ወር ተኩል ያህል በእስር ከቆዩ በኋላ ተለቀው ወደ አዲስ አበባ የመልስ ጉዞ ለማድረግ በቁ፡፡ ወይም ተገደዱ፡፡
*   *   *
“የስደታችን ትውስታ” መጽሐፍ ባለታሪኮች በከሸፈው የመጀመሪያ ጉዟቸው ተስፋ ቆርጠው የዕለት በዕለት ህይወታቸውን መግፋት አልጀመሩም፡፡ በጐንደር፣ በሐቲት ሁመራ አድርገው ገዳሪፍ ከዚያም ወደ ካርቱም አቀኑ፡፡ ካርቱም እንደገቡም የፖለቲካ ጥገኝነት ለማግኘት አስበው ለፖሊስ እጃቸውን ሰጡ፡፡ ዕቅዳቸውን ግን እንዳሰቡት በቀላሉ አልተሳካም፡፡ ወደ አነስተኛና ጠባብ ክፍሎች ተወርውረው ተቆለፈባቸው፡፡
ተስፋዬ ሁኔታውን እንዲህ ይገልፀዋል፡-
“በዚያች ትናንሽ የግንብ ክፍሎች ውስጥ ለየብቻ ተቆልፎብን በቀን ሦስት ጊዜ ዳቦና ውኃ በበሩ ቀዳዳዎች እየተሰጠን በቀኑ ሙቀትና በሌሊቱ ቅዝቃዜ መሰቃየቱን ተያያዝነው፡፡ በሌሎቹ ትናንሽ ክፍሎች ውስጥም እንደኛው ያሉ እስረኞች ከሚደርስባቸው ስቃይ የተነሳ ያለማቋረጥ የሚያሰሙትን ጩኸትና ኃይለ ቃላት ግንቡ እያስተጋባው ስንሰማ፤ የሚፈጠርብን ጭንቀትና የመንፈስ መረበሽ አሰቃቂ ነበር፡፡”
ከካርቱም ወደ አምድሩማን ተወስደው ከአምስት ወራት በላይ በእስር ቆይተዋል፡፡ ከእስር ከተፈቱም በኋላ ለአስራ ሶስት ወራት ያህል ካርቱም፣ ሱዳን ቆይተው፤ ተስፋዬ ጊዜያዊ የግሪክ ቪዛ በማግኘቱ ምክንያት ወደዚያው እንደተጓዘ ይተርካል፡፡
*   *   *
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመው መጽሐፍ፤ ደራሲ ተስፋዬ ዘርፉ ቀድመውት ግሪክ ገብተው ከነበሩ ወዳጆቹ ጋር ተገናኝቶ፤ ለአጭር ጊዜ ስራ አግኝቶ፤ በፕሪየስ ከተማ ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ህገወጥ መሆናቸው ታውቆ ፖሊስ እየፈለጋቸው የመሆኑ ዜና ሲደርሳቸው ከፕሪየስ ወደ አቴንስ ተጓዙ፡፡ ተጉዘውም ወደ ጀርመን ከሚሄዱ አሜሪካውያን ጋር በመቀላቀል ከዩጐዝላቪያ ድንበር ደረሱ፡፡ እዚያም ጥቂት ከቆዩ በኋላ ለቀናት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ በኋላ ግን ነፃ መሆናቸው ተነገራቸው፡፡ ከዚያም በዩጐዝላቪያ ፖሊሶች ትብብርና መሪነት ከጣሊያን ድንበር ደርሰው የእውር ድንብራቸውን እየተጓዙ ወደ ጣሊያን ገቡ፡፡
ተስፋዬ ከሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስቃይና በትግል የተሞላ ቆይታ በኋላ ወደ ዴንማርክ የመሄድ ዕድል አግኝቶ እስካሁን የሚኖርባት ሀገር ዜጋ ለመሆን እንደበቃ ማራኪ በሆነ ቋንቋና ትረካ የስደት ህይወቱን አብራርቷል፡፡ ወይም አውስቷል፡፡
*   *   *
ስደት የመከራ ቋት መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ግን ይህንንም እያወቁ ከመሰደድ ሊታቀቡ ወይም ሊገቱ አልቻሉም፡፡ እርግጥ ነው፤ ከፊት የተደቀነውን መከራና ስቃይ እያወቁ እራሳቸውን ወደ እሳቱ የሚጥሉ የመኖራቸውን ያህል፤ በወሬ ተደልለውና በደላሎች ተጭበርብረው የሚሄዱም አሉ፡፡
እውነቱን ለመናገር አሁን የሚታየው የስደት ሁኔታ መንግሥትን ከመተቸት የሚያድነው አይደለም፡፡ በሀገሪቱ የተንሰራፋው አድሎአዊ አሰራርና የተስፋፋው የስራ አጥነት ችግር ስር መስደዱ፤ እንዲሁም ስራ ለመያዝ የፓርቲ አባል መሆን እንደ መስፈርት መወሰዱ ወጣቶችን ጥርሱን አሹሎ ለሚጠብቃቸው የስደት አጋዘን ቀለብ አድርጓቸዋል፡፡
በዚሁ “የስደታችን ትውስታ” በተሰኘው መጽሐፍ መግቢያ ላይ የደራሲው ወዳጅና የስደት ውጣ ውረዱ ተካፋይ የነበሩት ዶ/ር ሙሐመድ ሐሰን ያሉትን በመጥቀስ ነገራችንን እንቋጨው፡፡ ዶክተሩ እንዲህ አሉ፡-
“(እኔና ደራሲው) ስደት መበረታታት አለበት የሚል ግንዛቤ የለንም፡፡ ይሁን እንጂ የሀገራችን ህዝቦች በአገኙት አጋጣሚ በየአቅጣጫው እንደሚሰደዱ የሩቅና የተረሳው ብቻ ሳይሆን በቅርቡ በዜጐቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ችግር በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ታዲያ ይህ የማያልቀው የስደት ሰቆቃ ማብቂያው መቼ ይሆን…?”
ይህ የሁላችንም ጥያቄ ነው!

Published in ህብረተሰብ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንትና… በቀደም ቲቪ ላይ ‘ትገኝበታለህ’ ብዬ ያልጠበኩህ ቦታ አየሁህሳ! የጨዋታው ህግ እንዲህ ሆኗል እንዴ! ሁለትና ከሁለት በላይ ወገኖችን ‘አታጣርስ’ እንጂ! ቂ…ቂ...ቂ… በነገራችን ላይ ምን መሰላችሁ… ዘንድሮ ነገርዬው በ‘ሁለት ባላ’ ብቻ መንጠልጠል ሳይሆን በሀያ ሁለት ባላ መንጠላጠል ሆኗል፡፡ ልጄ ሰዉ ሁሉ የጨዋታውን ህግ አውቆበታል፡፡
የምር ግን ቲቪ እኮ አንዳንዴ አሪፍ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ቢራ ላይ የቼ ጉቬራና የማልኮም ኤክስን ንግግሮች የሚያስንቅ ዲስኩር እያደረጉላችሁ ‘ተናግረው ካናገሯችሁ’ በኋላ፣ እዛኛው ‘የኮኑነት ቤት’ ውስጥ ስታዩዋቸው… አለ አይደል… ባለፉት ሦስት ወራት ‘ከአፋችሁ ያመለጣችሁን’ ሁሉ መለስ ብላችሁ ታሰላስላላችሁ፡፡ ሦስት ወር ያልኩትማ… ከሦስት ወር በኋላ ‘ይርጋ’ ሊኖር ይችላል ብዬ ነው። (ቂ...ቂ…ቂ…) እናማ…ቀን፣ ቀን ከእኛ ጋር ‘ብላክ ጠላ’ ማታ፣ ማታ ከሌሎቹ ጋር ‘ብላክ ሌብል’… አሪፍ ብልጠት አይደለም፡፡ በቲቪ ብልጭ ያልክብን ወዳጃችን ሆይ፣ ማሳሰቢያ አለን…ከዛሬ ጀምሮ ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር ትንፍሽ እንዳንል በነፍስ አባቶቻችን ግዝት እንደተጣለብን እወቅልንማ! ፈረንጅ… ‘ሴቲንግ ዘ ሬከርድ ስትሬት’ የሚለው ይህን አይደል!
እኔ የምለው... እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ሚዲያ ውስጥ ያለን ሰዎች ነገሮችን በደንብ ማየት ያለብን ጊዜ ላይ የደረስን አይመስላችሁም!
ይቺን ስሙኝማ…እንደ ፌዝም የሚያደርጋት ነገር ነች፡፡ የሆነ ጋዜጣ ያልሞተውን ሰውዬ መሞቱንና ግብአተ መሬቱ መፈጸሙንም ይጽፋል፡፡ ሰውየው በማግስቱ እዝግጅት ክፍሉ ይሄድና “ሳልሞት ሞቶ ተቀበረ ብላችኋልና ያለመሞቴን ገልጻችሁ ማረሚያ አውጡልኝ…” ይላል፡፡ አዘጋጁም ምን ይላል… “በፖሊሲያችን መሠረት አንዴ የወጣ ዜና ቢሳሳትም ማረሚያ አናወጣም…” ይላል፡፡ ሰውየውም “እንደዛ ከሆነማ ወደ ህግ እሄዳለሁ…” ሲል አዘጋጁ ምን ‘አስታራቂ ሀሳብ’ አመጣ መሰላችሁ… “ባይሆን ዳግም እንደተወለድክ አድርገን የልደት ዜናዎች ዓምድ ላይ እናወጣልሀለን…” ብሎት አረፈላችሁ፡፡
እናማ… ዘንድሮ ብዙ ማረሚያ የሚያስፈልጋቸው ስህተቶች እየተሠሩ እንደዋዛ እየታለፉ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…አንድ የሆነ አገር ውስጥ የሆነ ፖለቲከኛ የምርጫ ንግግር ሲያደርግ ምን አለ መሰላችሁ… “ተወዳዳሪያችን ፓርቲ አሥር ዓመት ሙሉ ስልጣን ላይ በቆየበት ዘመን አገሪቱን ሙልጭ አድርጎ በልቷታል፡፡ እስቲ አሁን ደግሞ ለእኛ ዕድሉን ስጡን…” ብሎ የምርጫ ቅስቀሳ አደረገ አሉ!
አሁን ለዚህ አርእስት አውጡ ብንባል…
‘የእንትን ፓርቲ እጩ አገሪቱን ሙልጭ አድርጎ ለመብላት ዕድል እንዲሰጣቸው መራጮችን ተማጸኑ…’
‘የእንትን ፓርቲ እጩ ከተመልካችነት ወደ ተጠቃሚነት ለመሸጋገር ህዝቡ ድምጽ በመስጠት እንዲተባበራቸው ጠየቁ…’
‘አገሪቱን ሙልጭ የማድረግ ዕድል ለሌሎቹም መዳረስ እንዳለበት የእንትን ፓርቲ እጩ ድምጽ ሰጪዎችን አሳሰቡ…”
ሰውየውን ወይንም ፓርቲያቸውን ጥምድ እድርጎ የያዘ አዘጋጅ ቢኖር ደግሞ… አለ አይደል… ሰውየው በስሜት እንዳሉ ፎቶ በትልቁ ያወጣና ርእሱን ደግሞ ምን ይለው መሰላችሁ… ‘አገሪቱ ካዝና ላይ የተጋረጠ አደጋ!’ ቂ…ቂ…ቂ…
እንዲህ አይነት የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርግ ‘ተወዳዳሪ’ ከገጠማችሁ ርዕስ በማውጣት ለመተባበር ፈቃደኞች መሆናችን ይታወቅልንማ! ወይ “ዕድል ስጡን…” ብሎ ነገር! ዕድል ከፈለገ ሎተሪ ይቁረጥ እንጂ ቦተሊካ ውስጥ ምን ጥልቅ ያደርገዋል!
ስሙኝማ…‘ቦተሊካ’ ውስጥ ዘው ካልን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…በዛ ሰሞን እንግሊዞቹ ቱባ፣ ቱባ ቦተሊከኞች ሰፊው ህዝብ ዘንድ ቀርበው በጥያቄ ሲፋጠጡ ቢቢሲ ላይ ላይቭ ሲያሳዩን ምን አልኩ መሰላችሁ… “ከዕለታት አንድ ቀን…” አልኩ፡፡ ልክ ነዋ… እንዲሁ ዝም ብሎ መራቀቅ አይደለማ…እኛ ሰፊ ህዝቦቹ ዘንድ ፊት ለፊት ቀርቦ ለጥያቄዎቻችን መልስ መስጠት ነዋ!       የምር… ቦተሊከኞች እኛ ፊት ቀርበው በጥያቄ ስናፋጥጣቸው ታየኝና “አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ያዢ...” ብዬ ተረትኩ፡፡
በአንድ ወቅት አንድ አለቃችን አንድ ስብሰባ ላይ ያሏት ነገር ትዝ ትለኛለች፡፡ ጋዜጠኛው የሆነ ሰልፍ ላይ አንዱን ተሰላፊ ይጠጋና… “የወንድሜን ስም ማን ልበል?” ይለዋል፡፡ ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው… “የወንድምህን ስም ራስህ እወቅ እንጂ እኔ የት አውቅልሀለሁ…” ‘አንጀት የሚያርስ’ መልስ አይደል!
እናማ… “የወንድምህን ስም ራስህ እወቅ እንጂ…” የምንባል ብዙ ነን፡፡
በሁሉም ሚዲያ ላይ ውስጥ ሊታረሙ የሚችሉ ብዙ ስህተቶች እየተሠሩ ነው፡፡
ኮሚኩ ነገር እኮ አሁን መሸወድ የማይቻልበት ዘመን እንደሆነ ነገሬ አለማለታችን ነው፡፡ በቂ የመመገቢያ ሳህን የሌለን ሁሉ ‘ሳተላይት ዲሽ’ የገጠምንበት ዘመን ነው፡፡ እናማ…ተደብቆ የሚቆይ ነገር የለም፡፡ ሃሎ…ይሰማል!
ስሙኝማ…ይቺን ካወራናትም እንድገማትማ። ‘ባለፈው ዘመን’ ነው፡. እናላችሁ…ወታደሩ ጦር ሜዳ ይቆስልና ሁለት እግሮቹን አጥቶ ሆስፒታል ይተኛል፡፡ ታዲያላችሁ…አንዱ ጋዜጠኛ ሲጠይቀው ምን ይለዋል… “ሁለት እግሮችህን በማጣትህ ምን ይሰማሀል?” አይነት ጥያቄ ይጠይቀዋል፡፡ ይሄ ነገር በሰሙት አካባቢ የሆነ ማጉረምረም ነገር ፈጥሮ ነበር። ሁለት እግር የማጣትን ያህል ጉዳት የደረሰበትን ሰው እንደዛ አይነት ጥያቄ መጠየቁ የምርም የሚዘገንን ነበር፡፡ ነገርዬውማ ምን መሰላችሁ…ጋዜጠኛው አስቀድሞ ‘እሱ የሚፈልገውን አይነት መልስ’ እንዲሰጠው አድርጎ መጠየቁ ነው፡፡ አለ አይደል… “ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡ ደግሞ ለአገሬ… አይደለም እግሮቼን ህይወቴን ብሰጥስ!” ምናምን እንዲለው ነበር፡፡
ዘንድሮም… አለ አይደል… በሁሉም ወገን እኛ የምንፈልገው መልስ እንዲሰጠን አመቻችተን የምንጠይቅ መአት ነን፡፡ ብዙ ‘ተጠያቂዎችም’…አለ አይደል…የሚፈልግባቸውን ስለሚያውቁት የእኛን የጠያቂዎቹን ‘አንጀት የሚያርስ መልስ’ ይሰጣሉ። ግንላችሁ… ዋናውን ነገር ብቻ እንሰማና እንደነገሩ ጣል የሚደረጉ ነገሮች ያልፉናል፡፡
“እንደሚያውቁት በአሁኑ ጊዜ የሠራተኞች መብት እየተጠበቀ ነው፡፡ አሠሪዎች እንደፈለጋቸው ሠራተኛን የሚበድሉበት ዘመን አልፏል፡፡ እርሶ ምን ይላሉ?”
“ተመስገን ነው እንጂ ሌላ ምን እላለሁ፡፡ ለመንግሥት ምስጋና ይግባውና አሁን መብታችን ተጠብቋል፡፡”
“አሁን እርሶ ምን ሥራ ላይ ነዎት?”
“ሥራ ላይ አይደለሁም
“ለምን
“ከነበርኩበት መሥሪያ ቤት አለአግባብ ተቀንሼ…”
ቂ…ቂ…ቂ…
“እማማ፣ ምን እያደረጉ ነው?”
“ለበዓል ዶሮ እየሸመትኩ…”
“እንደሚያውቁት በአሁኑ ጊዜ ዋጋ ለማረጋጋት በሚመለከታቸው ክፍሎች ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ በዚህም ለውጦች እየተመዘገቡ ነው፡፡ እማማ እርሶ ምን ይሰማዎታል?”
“ደስታ..ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡ ሌላ ምን ይሰማኛል፡ እሰዬው ነው፡፡”
“ለመሆኑ ዘንድሮ የዶሮ ዋጋ እንዴት ነው?”
“ሰማይ… ሰማይ ነው፡፡ እንደው ነጋዴውን ሀይ የሚለው ይጥፋ! ለበዓል ቤቱ ጭር እንዳይል ነው እንጂ፣ ባይገዛስ ቢቀር…”
ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…የምር ግን ሚዲያ ውስጥ ያለን አንዳንዶቻችን ምን ችግር ያለብን ይመስለኛል…አለ አይደል… ሰዉ የማያውቅ ይመስለናል፡፡ በቃ ሚዲያው በእጃችን ስለሆነ፣ ነገሮችን ለእኛ በሚመቸን መንገድ ብቻ ማቅረብ ስለምንችል… ድፍን አገር… “በእናንተ መጀን…” የሚል ይመስለናል። ሰዋችን ግን ያውቃል…በጣም ያውቃል፡፡ አይደለም ስለ አገር ጉዳይ ስለ ሶሪያ ጦርነት የእኛን መቶ እጅ የሚያስከነዳ ትንታኔ መስጠት የሚችል ሰው መአት መሆኑን ማወቅ ሸጋ ነው፡፡
እናማ…መቅደም እንኳን ባንችል ቢያንስ ከሰዉ ኋላ እንዳንቀር መሞከሩ አሪፍ ነው፡፡ እግረ መንገዴን…የስፖርቱ ነገርማ ግርም ይላል፡፡ ‘ከት ኤንድ ፔስት’ ሆኖ እንኳን… “ኧረ መቀሱ ይስተካከል!” እያልን ነው፡፡ የሚገጥሙን የትርጉም ስህተቶች… አለ አይደል…አይመቹም፡፡ ዲ.ኤስ.ቲቪ ቀን ማታ እየታየና እዛ ላይ መቶ ጊዜ ሲባሉ እየተሰማ እንኳን…‘ዋይኔ ሩኒ’ የሚባል ተጫዋች የለም ‘ዌይን ሩኒ’ ነው ሲባል መስማት አቅቶናል፣ ‘ሁል ሲቲ’ የሚባል ቡድን የለም፣ ‘ኸል ሲቲ’ ነው ስንባል መስማት አቅቶናል፡፡
እናማ… ቢያንስ ሰዉን መቅደም ቢያቅተን እንኳን ወደኋላ ላለመቅረት እንሞክርማ!
“የወንድምህን ስም ራስሀ እወቅ እንጂ…” ከመባል ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Published in ባህል