የታሪክ አፃፃፉ ምን ይመስላል? ደራሲው ታሪኩ የተፈፀመበትን ዘመን የተረዳው እንዴት ነው? መረጃዎቹን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከባህል… አንፃር እንዴት ነው የመዘነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ሚዛናዊነት መመዘን ይቻላል፡፡ ማነው መዛኙ ለሚለው ፀሐፊያንም አንባቢያንም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ታሪከ ፀሐፊ ፖለቲከኛ ሊሆን ይችላል። አንድን ታሪክ ሲጽፍ ምክንያታዊ መሆን ከቻለ ሚዛናዊ ታሪክ ፀሐፊ ነው ሊባል ይችላ

     ላለፉት 10 ዓመታት በየሁለት ሳምንቱ የመፃህፍት ላይ ውይይት ሲያካሂድ የቆየው ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ፤ በገጠመው ውስጣዊ ችግር ምክንያት የተለመደውን መድረክ ማዘጋጀት ካቋረጠ ስድስት ወራት ሆኖታል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የጀርመን ባህል ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ እና እናት ማስታወቂያ ድርጅት በጋራ በመሆን በወር አንዴ የመፃሕፍት ላይ ውይይት እንደሚያካሂዱ የተገለፀ ሲሆን የመጀመሪያው ዝግጅትም ባለፈው እሁድ በወመዘክር አዳራሽ ተከናውኗል፡፡
ለውይይት የተመረጠው “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” በሚል ርዕስ በአምባሳደር ዘውዴ ረታ ተጽፎ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሦስት ጊዜ ለመታተም የበቃው መጽሐፍ ሲሆን፤ ለውይይት የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ አበባው አያሌው ነበሩ፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከአገር ውጭ በመሆናቸው በዕለቱ ሊገኙ አልቻሉም፡፡
“የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ዘመን በአገሪቱ በርካታ ታሪኮች የተከናወኑበት በመሆኑ ልዩ ወቅት ነበር፡፡ ዘመናዊ ለውጥ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ተጀመረ የሚሉ አሉ፤ በተግባር የታየው ግን በአፄ ኃይለሥለሴ ጊዜ ነው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አወዛጋቢ ንጉሥ ነበሩ፡፡ የሚያደንቋቸው አሉ፡፡ በኋላ በአገሪቱ ለታየው ምስቅልቅል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለው የሚከሷቸውም አሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ የተፃፈ ቢሆንም ወደፊትም ብዙ የሚፃፍበት ይመስላል፡፡ አብዮተኞቹ ታሪክ ፀሐፊዎች አፄ ኃይለሥላሴን ሲያጠለሹ፤ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ውስጥ ያገለገሉ ታሪክ ፀሐፊዎች ያሞግሷቸዋል፡፡ ሦስተኛው ዓይነት ታሪክ ፀሐፊዎች የውጭ አገር ሰዎች ሲሆኑ የተደረገውን ሐቅ ከማስቀመጥ ውጭ ነገሩ ጥሩ ነው፣ መጥፎ ነው ብለው ትንታኔ ውስጥ አይገቡም፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህ ሚዛናዊ ሆነው ይታያሉ።”
በዚህ መልኩ ገለፃ የጀመሩት አቶ አበባው አያሌው፤ የአምባሳደር ዘውዴ ረታን መጽሐፍ የቃኙት በሰባት መመዘኛዎች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ደራሲው ለጉዳዩ ያላቸው ቅርበት ምን ይመስላል? የመረጃ ምንጫቸው ምን ነበር? መረጃዎቹስ በመጽሐፉ ውስጥ በምን ያህል ተንፀባርቀዋል? ሚዛናዊነቱ ምን ይመስላል? በመጽሐፉ የተገለፀው ዘመን ታሪክ ምን ያህል ሙሉ ሆኖ ቀርቧል? የታሪክ ሃተታውና የቋንቋ አጠቃቀሙ ምን ይመስላል? መጽሐፉ ምን አዲስ ነገር አሳወቀን?
እነዚህን ጥያቄዎች አንስተው ምላሽ በመስጠት ማብራራት የቀጠሉት የዩኒቨርሲቲው ምሁር፤ የአገርም ሆነ የግለሰቦች ታሪክ በአንድ ሰው ብቻ ተጽፎ እንደማያበቃ ጠቁመው በአፄ ኃይለሥላሴ ዙሪያ 56 ያህል መፃሕፍት መታተማቸውን ገልፀዋል፡፡
ደራሲው ለፃፉበት ርዕሰ ጉዳይ ቅርበት ነበራቸው፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰራተኛ፣ የቤተ መንግሥት ጋዜጠኛና በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ  ከመሆኑም ባሻገር በአምባሳደርነትም ተሹመው መስራታቸው የቃል፣ የሰነድና የፎቶግራፍ መረጃዎችን ለማግኘት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው አቶ አበባው ገልፀዋል፡፡
አምባሳደር ዘውዴ ረታ በአገር ውስጥና በውጭም መረጃዎችን ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ያገኙትን በጥንቃቄ ማስቀመጥ በመቻላቸው “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በሚገባ ተጠቅመበውበታል፡፡ በአገር ውስጥ ከጽሕፈት ሚኒስቴር ሰነዶችን በቀጥታ አግኝተዋል። በዘመኑ ታላላቅ ባለስልጣናት ከነበሩት መኮንን ሀብተወልድ፣ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ፣ ይልማ ደሬሳ ከመሳሰሉት ቤተሰቦችም ብዙ መረጃ ሳያኙ አልቀሩም ተብሏል፡፡
“የቃል መረጃም በብዛት ተጠቅመዋል፡፡ ይህ በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነው፡፡ ምስክርነቱን የሰጠው ሰው ማነው? የፖለቲካ አመለካከቱ፣ ዕውቀቱ … መጠየቅና መጣራት አለበት። የቃል ምስክርነት እውነታነቱ ሌላ ማመሳከሪያ ካልተገኘለት ለዘመን ፍርድ ክፍት ተደርጎ የሚተው ነው” ያሉት አቶ አበባው፤ በተመሳሳይ በዚህ መልኩ ጥያቄ አስነስቶ እስካሁንም እያነጋገረ  ነው በማለት “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” የተሰኘውን መጽሐፍ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
የቃልና የሰነድ መረጃዎች በስፋት ጥቅም ላይ ውለውበታል የተባለው “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” መጽሐፍ፤ በማጣቀሻነት የተጠቀማቸው መፃሕፍት ቁጥር ትንሽ እንደሆኑና የመረጃ አገላለጽ ችግር እንደሚታይበት ተጠቁሟል፡፡ የመረጃ ምንጩ ሰውም ይሁን ሰነድ የት እንደሚገኝ መገለጽ አለበት። በመጽሐፉ ላይ አባሪ ማኖር ገጽ ያበዛል ተብሎ ከተፈራ መረጃዎች ከየትኛው ሰነድ እንደተወሰዱ በግርጌ ማስታወሻ ቢገለጽ ጥሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ደራሲው ያገኘውን ምንጭ አንባቢያንም እንዲደርሱበት ያግዛል ተብሏል፡፡ መጽሐፉ በርካታ ፎቶግራፎችን ቢይዝም “የኤርትራ ጉዳይ” ከሚለው መጽሐፋቸው ጋር ሲነፃፀር ይኸኛው መጽሐፍ የያዛቸው ፎቶግራፎች ቁጥራቸው ማነሱም ተገልጿል፡፡
“የታሪክ ጠላት ፖለቲካ ነው፡፡ ፖለቲካ ታሪክን ወደራሱ ፍላጎት ይዞት ይሄዳል፡፡ ከዚህ አንፃር አምባሳደር ዘውዴ ረታ በመጽሐፋቸው ምን ያህል ሚዛናዊ መሆን ችለዋል?” ያሉት ምሁሩ፤ ደራሲው በአንዳንድ ቦታ ኃይለሥላሴን ከብዙ ነገሮች ነፃ ሲያደርጓቸው ይታያል፡፡ የታሪክ ፀሐፊ አይበይንም። ፍርዱን ለአንባቢያን ነው መተው ያለበት፡፡ እንዲህም ሆኖ መጽሐፉ ባነሳው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በአገር ውስጥ የነበረውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሁኔታና ተጽዕኖንም እያመሳከረ ታሪኩን ሚዛናዊ ለማድረግ ሞክሯል ተብሏል፡፡
ከ1923-1948 ዓ.ም ያለውን ዘመን ማዕከል አድርጎ የተዘጋጀው የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ፤ የ25 ዓመታቱን ታሪክ በምን ያህል መጠን ሙሉ አድርጎ አቀረበ? ለሚለውም ጥያቄ የአምስቱ ዓመት የአርበኞች ተጋድሎ ታሪክ አለመፃፉ (ደራሲውም ይህንን በመጽሐፉ መግቢያ አንስተውታል)፤ አፄ ኃይሥላሴ በስደት በእንግሊዝ በነበሩበት ጊዜ አኗኗራቸው ምን ይመስል እንደነበር አለመገለፁ፤ ከድል በኋላ አርበኞች፣ ባንዳዎች፣ ስደተኞች፣ ምሁራን በውስጣቸው የነበረው ትግል ምን እንደነበር አለመብራራቱ፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አውሮፓውያን ለስደተኛ መንግሥታት ዕውቅና ሲሰጡ ኢትዮጵያ ዕድሉ ስለመነፈጓ በስፋት አለመፃፉ … የመሳሰሉት የመጽሐፉን ሙሉእነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል ብለዋል - አቶ አበባው፡፡
መጽሐፉ በታሪክ አተራረክና በቋንቋ አጠቃቀሙ የተሳካለት መሆኑን የመሰከሩት አቶ አበባው  መጽሐፉ ምን አዲስ ነገር አሳየን? ለሚለውም “ትኩረት ያልተሰጣቸው ጥቃቅን ነገሮችን አሳይቶናል፡፡ ማን ምን ብሎ ጠይቆ፤ ማን ምን ብሎ መለሰ የሚለውን ሁሉ እናይበታለን። የ1923ቱ ሕገ መንግሥት ሊፀድቅ በሂደት ላይ እያለ በዘመኑ ምሁራንና ባለስልጣናት መሐል የተደረገውን ሰፊ ክርክር አቅርቦልናል (የሞኝ ዘመን መጽሐፍ ሆኖ ነው እንጂ በህገ መንግሥቱ ዙሪያ የቀረበው ርዕስ ብቻ አንድ መጽሐፍ ይወጣው ነበር)፡፡ በሊግ ኦፍ ኔሽን የተደረገውን ክርክር በተመለከተ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ሰዎች ዘንድ ያለው አመለካከት ምን ይመስል እንደነበር በስፋት ገልጿል፡፡ ስለ መኮንን ሀብተወልድ፣ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ፣ ይልማ ደሬሳ ካሁን ቀደም የማናውቃቸውን አዳዲስ መረጃዎች ሰጥቶናል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ምን ያህል ውጤታማ (በባሩድ ሳይታጠኑ በንግግርና ውይይት በማሳመን) መሆናቸውን አይተንበታል፡፡ መጨረሻ ላይም የንጉሠ ነገሥቱ ምኞት፣ የምሁራኑ ፍላጎትና የባለሥልጣናቱ መሻት መለያየቱንና ሁሉም ብቻውን መቆሙን አመላክቶናል፡፡” ብለዋል፡፡
አቶ አበባው መጽሐፉን አስቃኝተው ከጨረሱ በኋላ ከተሰብሳቢዎች የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ አንዳንዴ በሚጽፉት ስሜታዊ ገለፃ ፀሐፊ ትዕዛዛትን ይመስላሉ፡፡ በዚህ ላይ የምትለን ነገር አለ? ደራሲው የታሪክ ሰው አይደሉም፤ አምባሳደር (ዲፕሎማት) ናቸው የሚሉ ክርክሮች አሉ፡፡ ማረፊያው የቱ ነው? ታሪክን ፖለቲካ ስለሚጎትተው ታሪክ ፀሐፊ ሚዛናዊ እንዲሆን እንዴት ይጠበቃል? ታሪክ ፀሐፊ ይመዘናል ከተባለ፤ መዛኙ ማነው? ታሪክ ፀሐፊው ላይ የቀረበው አድናቆትና ነቀፌታን ለመዳኘት ዲስፕሊኑ ከየት ነው የሚገኘው?
ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ የሰጡት አቶ አበባው አያሌው፤ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” የተሰኘው መጽሐፍ የንጉሡ ታሪክ ላይ ትኩረት ቢያደርግም አምባሳደር ዘውዴ ረታ ጸሐፊ ትዕዛዝ አይደሉም ብለዋል፡፡ በተፈጥሮም የተገኘ ይሁን በልምድ አተራረክና አቀራረቡ ጥሩ የሆነ መጽሐፍ አቅርበውልናል፡፡ ታሪክን ማንም ይጽፈዋል። ፀሐፊዎቹም ህዝባዊና ሙያዊ ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ተነባቢነት ያላቸው አብዛኞቹ የታሪክ መፃሕፍት የተፃፉት በጋዜጠኞች ነው፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስለሰሩ የታሪክ መጽሐፉ ለመፃፍ ችለዋል፡፡
“በታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ሚዛናዊነት መኖሩን የምናረጋግጠው ደራሲው ምን መረጃ አገኘ? መረጃውን እንዴት አቀረበው? አተረጓጎሙስ እንዴት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎችን በማንሳት፤ ጥያቄዎቹ የሚተነተኑበትን ሂደት ተከትሎ በመመርመር ነው። የታሪክ አፃፃፉ ምን ይመስላል? ደራሲው ታሪኩ የተፈፀመበትን ዘመን የተረዳው እንዴት ነው? መረጃዎቹን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከባህል… አንፃር እንዴት ነው የመዘነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ሚዛናዊነት መመዘን ይቻላል፡፡ ማነው መዛኙ ለሚለው ፀሐፊያንም አንባቢያንም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ታሪከ ፀሐፊ ፖለቲከኛ ሊሆን ይችላል። አንድን ታሪክ ሲጽፍ ምክንያታዊ መሆን ከቻለ ሚዛናዊ ታሪክ ፀሐፊ ነው ሊባል ይችላል” በማለት አቶ አበባው ማብራሪያቸውን ቋጭተዋል፡፡      

Published in ጥበብ

 ይሄን ጉዳይ ይዘን ወደኛ አገር ስንመጣ፣ ምን እንገነዘባለን? እውነት ልቦለድ እያጣጣረ ነው? ወግ እያንሰራራ ነው? ግለ ታሪክስ? ልቦለድ ለሞት ይሁን ለእንቅልፍ፤ ባለየለት ሁኔታ እያንጐላጀ ነው፡፡ ንቃት አይሰማውም፡፡ አዳም ረታ በ “መረቅ” የቀሰቀሰው መስሎን ነበር፡፡ መልሶ ተኛ፡፡ ይስማዕከ ወርቁ በ  ልቦለዱ የዘርፉን ሞተር ሳይቀሰቅስ ማለፉ ሌላው የሥጋት ምንጭ ነወ፡፡ ከዚያስ? ምንም

      ተፈጥሮ ጋጠ - ወጥ አይደለችም፡፡ የምታከብረውና የምታስከብረው ህግ አላት፡፡ እርስበእርስ የሚናበብ ድንጋጌ፤ የማይዛነፍ፣ የማይንከረፈፍ ስድር ሥርዓት አላት፡፡ እንደ ሰዎች ህግ ተደብቀው የማይጥሱት፣ እሳት በላሰ ጠበቃ የማይሞግቱት፣ በጉቦ የማይቀለብሱት…ይሄንን የተፈጥሮ ህግ ፓይታረጐስ (Pythagoras) “ኮስሞስ” (Cosmos) ይለዋል፡፡ ሔራክሊተስ ደግሞ “ሎጐስ” (Logos) በሚል ይጠራዋል፡፡ ከእነሱ ሁሉ በኋላ የመጣው ሂዩም (Hume) ደግሞ “የተፈጥሮ ህግ” (Laws of nature) ሲል በጥሬው ያመለክተዋል፡፡
የተፈጥሮ ህግ ዘንድ ሥርዓተ አልበኝነት አይታሰብም፡፡ ሥርዓተ - አልበኝነት የተፈጥሮ እንቅፋት ብቻ ሳይሆን ፀርም ጭምር ነው፡፡ ከዛፍ የወደቀውን አንዱን ሰብራ ሌላውን አትምርም፤ ያልበላውን ከመራብ፣ ያልጠጣውን ከመጥማት አትዛነፍም፡፡ ብርሃን የሌለበት አናይም፣ ድምጽ ያልነዘረበት አንሰማም፣ ያልጐረሰውን አንቀምስም…
…የሰው ልጅ እንጂ ተፈጥሮ ከሰው ልጅ ጋር ለመግባባት መንገድ አትቀይስም፡፡ የልብ ምታችንን ሰከንድ ቆጣሪ አይተካውም፡፡ ረሃባችን ሰዓት ቆጣሪ እየተከተለ አይደውልም፣ ልደታችን በካላንደር ድንጋጌ እርምጃውን አይተካም፡፡ በህይወት የመቆያ ጊዜአችን የተባበሩት መንግሥታትን ያገናዘበ አይደለም፡፡ እኛ እንጂ ተፈጥሮ ከኋላ አይደለችም፡፡
ውኃ አንዳንዴ በመቶ ሌላ ጊዜ በአምስት መቶ ዲግሪ አይፈላም፡፡ መዘላበድ የሰው እንጂ የተፈጥሮ አይደለም፣ አድርባይነት የእኛ እንጂ የእሷ አይደለም … እንኳን እኛ ፈጣሪዋም በተፈጥሮ ህግ ሥር ነው፡፡  
መስሏት እንጂ መስላው አትኖርም፡፡ የሰው ልጅ ኮምፒዩተርን ስለፈጠረ ከኮምፒዩተር ህግና ከተጫነው ፕሮግራም ውጭ ማዘዝ ይችላል? እንዲያ ነው!!
ግን ደግሞ …
በተአምርና በተረት መሰል ዘመን ውስጥ እንገኛለን፡፡ ዴቪድ ሺልድ የተሰኘ ፀሐፊ “Fictions times” ይለዋል፡፡ ልቦለዳዊ፣ ምናባዊ፣ የፈጠራ መሰል ዘመን ለማለት ነው፡፡ እስኪ አካባቢያችንን እንመልከት፡፡ ከምንም ጋር ባልተገናኘ ኩርማን ብረት ዓለም ጫፍ ያለ ሰው እናነጋግራለን፤ ቦታው ላይ ሳንገኝ ክንውኖችን በቀጥታ እናያለን፤ ብረት ቀጣጥለን እናዛለን፣ እንበራለን፣ በምድር እንሽከረከራለን፤ በርቀት መቆጣጠሪያ ሁሉን እናከናውናለን…እኛ ለጥንቱ ዘመን ሰው ምንድነው?
“Human Cloning” ላይ እስክንደርስ ሔዋን ከአዳም ግራ ጐን መገኘቷ ምክንያት አልባ፣ የእግዚአብሔር ብቻ ተአምር ነበር፡፡ የመብረር ጥበብ እስኪከሰት የኤሊያስ የእሣት ሰረገላም የተፈጥሮ መታዘዛዊ ተአምር ነበር፡፡ ኒውክሊየር እስኪፈጠር የሶዶምና ጐሞራህ በእሳት ባህር መጥለቅለቅ ሩቅ ነበር፡፡ ባዮሎጂካል ጦር መሣሪያ እስክናይ የግብፆች መቆሳሰል ታላቅ ተአምር ነበር፡፡
ዛሬ እነዚህ ሁሉ ተአምሮች የሚከናወኑበት ተረትና ልቦለድ መሰል ዘመን ላይ ነን፡፡ “ስለዚህ ሌላ ተረትና ልቦለድ አያስፈልገንም” ይላል ዴቪድ ሺልድ “Reality Hunger፡ A manifesto” በተሰኘ ሥነ - ፅሁፋዊ ጥናቱ፡፡ “ፈጠራ ያልሆኑ እውነተኛ የጥበብ ሥራዎችን እንወዳለን፤ ምክንያቱም ምናባዊ ልቦለድ በመሰለ ጊዜ ውስጥ ስለምንኖር” (We like nonfiction because we live in fictitious times)
በዚህ ዘመንና ቴክኖሎጂ አመጣሽ ህይወት ሳቢያ አደጋ የተጋረጠበት የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ረጅም ልቦለድ እንደሆነ ጥናቱ ላይ በአጽኖት ተጠቅሷል፡፡ “Good bye to the Novel, 2015 will be the year of the Essay” በሚል ርዕስ ኒውስዊክ መፅሔት ላይ ባለፈው ጥር ወር ሺልድ ባቀረበው መጣጥፍ የያዝነው አመት በእውነታ ላይ የተመሠረቱት ወግ (essay)፣ ግለታሪክ በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ ሆነው መገኘታቸው የልቦለድ ግብአተ መሬት መፈፀሙ አይቀሬ መሆኑን ይጠቁማል ይላል፡፡
ይሄን ጉዳይ ይዘን ወደኛ አገር ስንመጣ፣ ምን እንገነዘባለን? እውነት ልቦለድ እያጣጣረ ነው? ወግ እያንሰራራ ነው? ግለ ታሪክስ? ልቦለድ ለሞት ይሁን ለእንቅልፍ፤ ባለየለት ሁኔታ እያንጐላጀ ነው፡፡ ንቃት አይሰማውም፡፡ አዳም ረታ በ “መረቅ” የቀሰቀሰው መስሎን ነበር፡፡ መልሶ ተኛ፡፡ ይስማዕከ ወርቁ በ     ልቦለዱ የዘርፉን ሞተር ሳይቀሰቅስ ማለፉ ሌላው የሥጋት ምንጭ ነወ፡፡ ከዚያስ? ምንም
በሌላ በኩል በሺልድ እንደተጠቆመው፤ በእኛም አገር ያለፉት ጥቂት አመታት የወግ እና ግለታሪክ መጽሐፍት “ይዞላቸው” ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከፍተኛውን የገበያ እርከን ከተቆናጠጡት መፃሕፍት መካከል አብዛኞቹ (በሙሉ ላለማለት) መጣጥፍ ወይም ግለታሪክ ናቸው፡፡ “ፒያሳ ሙሐሙድ ጋ ጠብቂኝ”፣ “ሮዛ”፣ “የአዲስ አበባ ጉዶች”፣ “ታወር ኢን ዘ ስካይ” ፣ “ፈተና”፣ “የሐበሻ ጀብዱ”፣ “አሥራ ሰባት መድፌ” ወዘተ
ገበያው በሩን ገልጥጦ ባይቀበላቸውም መልካም ፊት ያልነፈጋቸውም መጽሐፍት ቢሆኑ እዚያው መጣጥፍና ግለታሪክ ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ “የይሁዳ ድልድይ”፣ “እኛ የመጨረሻዎቹ”፣ “የሰማይ ላይ ማማ”፣ (የገብሩ አስራት)
ህይወት ወደ ምናብነት ስትኮበልል፣ የንባብ ፍላጎት ወደ እውነታ አፈግፍጓል፡፡ መጣጥፍና ግለ-ታሪክ መፈለጋቸው ለዚህ ነው፡፡ ህይወት እውነታ በነበረበትና የተፈጥሮ ህግ በበላይነት በረበበት ዘመን የሰው ልጅ የንባብ ፍላጎቱ ወደ ምናባዊ ልቦለድ ያደላ እንደነበር እሙን ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ ዛሬም ቢሆን የተፈጥሮ ህግ ውሉን አላላላም፡፡ ይሁንና የተፈጥሮ ህግ በግትርነት የሚጠብቀውን መግቢያ በር የሰው ልጅ በአሳባሪ አልፎ ከበስተጀርባው ያሻውን እየሆነና እየሰራ ነው፡፡
ተፈጥሮ ጋጠ-ወጥ ባትሆንም፣ የምታከብረውና የምታስከብረው ህግ ቢኖራትም፣ እርስ በእርስ የሚናበብ ድንጋጌ ላይ ብትቆምም የማይዛነፍ፣ የማይንከረፈፍ ስድር ስርዓት ብታቆምም ሳይንስን ተገን አድርጎ ሽምቅ በወጋት የሰው ልጅ ሳታውቀው እጇን ሰጥታለች፡፡ በእውነታ የቀነበበችው የሰው ልጅ አፈትልኮ ተረትና ምናባዊ ዓለም ውስጥ ገብቷል፡፡ በመሆኑም የዚህን ተቃራኒ በእውነታ ላይ የተመሰረተ የጥበብ ስራ ሽቷል፡፡ እዚህ መሃል ሙሉ ለሙሉ ምናብ ላይ የተመሰረተው ልቦለድ ዕጣ - ፈንታው ምንድንነው?
“ሞት!” ይላል ዴቪድ ሺልድ በጥናቱ፡፡
“የመዳን፣ የማንሰራራት ዕድል የለውም?”
“አለው”
“እንዴት?”
“ልቦለድ በጭብጥ ሳይሆን በቅርፅ(Form) ብቻ ከብዙዎቹ ይለያል፡፡ ይሄንን የቅርፅ ጉዳይ በህይወት ለመቆየት ሲል መተው ይኖርበታል፡፡ ከተንዛዛ ገለፃ ቀጥታ ጉዳዩን በአጭር መንገድ ወደ መንገር መሸጋገር ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዘመኑ ግድ ያለውን የወግ፣ የግለ ታሪክ ባህርያት በመውረስ ወደ እውነታ ድብልቅ ምናብ መምጣት አለበት፡፡” ይላል በአጠቃላይ፡፡
ሺልድ ይሄን ያለው ከአራት አመታት በፊት ባቀረበው ጥናት ላይ ነበር፡፡ ይሁንና ልቦለድ ከምናብነት ወጥቶ ከውነታ ጋር በመደባለቅ የወግ (essay)፣ የግለ ታሪክ (Autography) እና ትውስታ (Memoir) ባህርይ መያዝ ከጀመረ አስርት ዓመታት እያስቆጠረ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የቼኩን ደራሲ የሚላን ኩንዴራ (Milan Kundera) ሥራዎች ማየት ይበቃል፡፡ “The Book of Laughter and Forgetting” የተሰኘው ልቦለዱን ፅፎ ያቀረበው በ1978 ዓ.ም ነበር፡፡ ይሄ ልቦለድ የወግ፣ የግለታሪክ፣ የትውስታ፣ የምናብ ድብልቅ ነው፡፡ “The Unbearable lightness of being” የተሰኘ ስራውም ተመሳሳይ ባህርይ ከመያዙም በላይ ፍልስፍናን አካትቶ በዚው ዘመን አካባቢ ወጥቷል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ ስራዎችም አሉት፡፡
ኩንዴራ “The book of Laughter and Forgetting” ውስጥ ነባሩ የልቦለድ ጠባይ የማይፈቅደው ብዙ ወግ መሰል ፅሁፎች ተካትተው ይገኛሉ፡፡ በፖለቲካ ረገድ እራሱ ደራሲው የነበረውን የለውጥ ውጥንቅጥ እንዳለ ተርኮታል፡፡ በተለይ ሩሲያ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ አገሩን (ቼክን) ስትቆጣጠር እርሱ ላይ ደርሶ የነበረውን መከራ እንደወረደ ይተርከዋል፡፡
ወደኛ አገር ልቦለድ እንምጣ
ልቦለዱን ከነባር ታሪክና ከተከናወነ ድርጊት ጋር ደባልቆ የማቅረብ ሥራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረ ነው፡፡ ቀደም ሲል እነ ብርሃኑ ዘሪሁን (የታንጉት ምስጢር) የተሳተፉበትና አሁንም በሀብታሙ አለባቸው (“አውሮራ” እና “የቄሳር እንባ”) የተቀጠለበት ልቦለዳዊ ዘውግ፤ “ታሪካዊ” የሚሰኝ ነውና እዚህ የሚካተት አይደለም፡፡ ልክ በኩንዴራ ስልት የአማርኛ ልቦለድን የተቀላቀሉ ወጣት ደራሲያን ግን አልጠፉም፡፡ የመጀመሪያው በዕውቀቱ ስዩም “እንቅልፍና እድሜ”ን ይዞ በመምጣት ገድ ብሎናል፡፡ ቀጥሎም “በመግባትና መውጣት” መቀጠል እንደሚችል አሳይቶናል፡፡
ከበዕውቀቱ በመቀጠል ጥቂት የማይባሉ ወጣት ደራሲያን ከምናብ የተፋታ እውነት ቀመስ ልቦለድና አጫጭር ልቦለድ አቅርበውልናል፡፡ አሌክስ አብርሃም፤ “ዶ/ር አሸብር”፣ ሌሊሳ ግርማ “የንፋስ ህልሞች”፣ የአሸናፊ ውዱ “ሚስት መሆን” … እና ሌሎቹንም ከዚህ የኩንዴራ ዘውግ አንፃር እየተመለከትን ሳምንት እንተነትናለን፡፡ እስከዚያው ቸር ይግጠመን፡፡   

Published in ጥበብ

      በበረከት ማቱሳላና በሰማኸኝ ደሳለኝ በእንግሊዝኛ ቋንቋ “Exodus South Ethiopia Travel Guide Book” በሚል ርዕስ ተፅፎ በኤክሰደስ ፕሮሞሽን ማስታወቂያ ስራ ድርጅት አሳታሚነት የታተመው የጉብኝትና የጉዞ መመሪያ መፅሀፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ፡፡ መፅሀፉ በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦችን፣ ከ30 በላይ ከተሞችን፣ የባሌ ተራራን ጨምሮ 12 ብሄራዊ ፓርኮችን የሚያስቃኝ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ለቱሪስቶች ጠቃሚ የሆኑ የጉዞ ምክሮችን እንዳካተተም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 202 ገጾች ያለው በየሃገሩ የሚገኙ የማፊያና የአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን እንዲሁም በአደጋ ጊዜ ተጠሪ የሆኑ ተቋማትን የስልክ አድራሻ አካቶና የተሰናዳ የቱሪስት መረጃ መፅሀፍ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ መፅሀፉ በ17 ዶላር፣ በ15 ዩሮ እና በ14 ፓውንድ ለገበያ መቅረቡም ተገልጿል፡፡

  በደራሲ ዘውዱ ደስታ የተሰናዳው “ሳንሱሲ” የተሰኘው ልብወለድ መፅሐፍ በዚህ ሳምንት ለንባብ በቃ፡፡ መፅሐፉ ታሪካዊ ጉዳዮችን በሁሉም ዘመናት አነጋጋሪ በሆኑት ፎቶዎች የማይታዩ እጆች ላይ ተመርኩዞ ሀገራዊ ትልልቅ የግንባታ ሂደቶችን እያዋዛ ይዳሰሳል፡፡ “ሳንሱሲ” በ334 ገፅታ የተመጠነ ሲሆን በ136 ገፆች ዋጋ ለገበያ ቀርቧል፡፡
መፅሐፉ በቅርብ ቀን የኪነ-ጥበብ ባለሚያዎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት ይመረቃል፡፡

  በጋዜጠኛ ዳንኤል ብርሃኑ ተሾመ የተዘጋጀው “የማስታወቂያ መሰረታዊ መርሆዎች” የተሰኘ መጽሃፍ ሰሞኑን ለገበያ የቀረበ ሲሆን ከትላንት በስቲያ ምሽት በራስ ሆቴል አዳራሽ ተመርቋል፡፡
 በሻማ ቡክስ አሳታሚነት ለንባብ የበቃው መፅሀፉ፤በተለይም የሬዲዮና ቴሌቪዥን ማስታወቂዎች ላይ በማተኮር በጥናት ላይ ተመስርቶ እንደተዘጋጀም ታውቋል፡፡ ከትላንት በስቲያ በመፅሀፉ ምርቃት ላይ የማስታወቂያ ባለሙያዎችና የማስታወቂያ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተው፣በመፅሀፉ ይዘትና ጠቀሜታ ዙሪያ ሙያዊ አስተያየትና ገለፃ ማድረጋቸውም ታውቋል፡፡ 

ከወር በፊት በጋለሪያ ቶሞካ በተከፈተው “ውስጣዊ ግለትና እንፋሎት” የተሰኘ የስዕል ትርዒት ላይ ነገ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ በቶሞካ ውይይት እንደሚካሄድ ዳይሬክተሩ ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ ገልጿል፡፡ የወጣት አሸናፊ ማስቲካ ስራዎችን በ14ኛው ዙር የስዕል ትርዒቱ ለእይታ ያቀረበው ጋለሪው፤ ሳር ቤት ካናዳ ኤምባሲ ፊት ለፊት በሚገኘው ጋለሪያ ቶሞካ በርካታ የስዕል አፍቃሪያን፣ ሰዓሊያን፣ ጋዜጠኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት ከ35 በላይ በሚሆኑ የወጣቱ ሰዓሊ ስራዎች፣ የአሳሳል ዘይቤና በስዕል ፍልስፍናው ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

   በኢንሽዬቲቭ አፍሪካ መካሄድ የጀመረው አዲስ ኢንተርናሽናል ዘጋቢ ፊልም ፌስቲቫል ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ  እንደሚካሄድ ኢንሼቲቭ አፍሪካ በላከው መግለጫ አስታወቀ፡፡
የፊልም ፌስቲቫሉ በዋናነት በዓለም ላይ ያሉ እውታዎችን ለማንፀባረቅና የተለያዩ ተግዳሮቶችን ለመመልከት የሚያስችሉ ዘጋቢ ፊልሞች ተመርጠው ለእይታ የሚቀርቡበት ሲሆን በተለይም በአሁኑ ወቅት የሚታየው የቴክኖሎጂ ምጥቀት ዓለምን እያስተሳሰረ ባለበት ወቅት አገራችን ከዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ ሆና በየጊዜው ያለው ለውጥ ለተመልካቹ እንዲደርስ ለማድረግ የቅርብ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ (የቴክኖሎጂ ሽግግር የተንፀባረቀባቸው) ዘጋቢ ፊልሞች ለእይታ ይቀርቡበታል ተብሏል፡፡
ፊልሞቹ በዋናነት በአካባቢ ደህንነት፣ በህገወጥ ሰዎች ዝውውር (ስደት)፣ በትምህርት እና በስነፆታ፣ ባህልና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን በዘንድሮ ፊልም ፌስቲቫል ላይ 60 ያህል በተለያዩ ፌስቲቫሎች ላይ ተሸላሚ የሆኑ ዘጋቢ ፊልሞች መመረጣቸውን ኢንሽዬቲቭ አፍሪካ ገልጿል፡፡ ከተመረጡት ዘጋቢ ፊልሞች መካከል “Citizen Four”፣ “Concerning Violence”፣ “Evaporating Board” እና Elephant Dream” እንደሚገኙበት የታወቀ ሲሆን ፌስቲቫሉ አምስት ኪሎ በሚገኘው በብሄራዊ ሙዚየም በቅርስ ጥናትና ምርምር አዳራሽ ሰኔ 5 ተከፍቶ እስከ ሰኔ 9 ለተመልካች እንደሚቀርብ ድርጅቱ ከላከው መግለጫ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፌስቲቫሉ ከቅርስ ጥናትና ምርምር አዳራሽ በተጨማሪም በሀገር ፍቅር ትንሿ አዳራሽ፣ በብሪቲሽ ካውንስልና በአሊያንስ ኢትዮፍራንሴዝ ለእይታ እንደሚቀርብ ተገልጿል፡፡

 የዜማ ብዕር ኢትዮጵያ የስነ-ፅሁፍ ማህበር አባል በሆነችው ወጣት ገጣሚ ፍሬዘር ዘውዱ ተፅፈው የተሰናዱ በርካታ ግጥሞችን የያዘው “የፍቅር ገፆች” የግጥም መድበል ትላንት ከረፋዱ 3፡00 እስከ 6፡00  በብሄራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ የስብሰባ አዳራሽ ተመረቀ፡፡
በፍቅር ላይ ያተኮሩ ግጥሞችና ደብዳቤዎችን በያዘው በዚህ የግጥም መፅሀፍ ምርቃት ላይ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን ተገኝተው ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን ከመፅሀፉ የተመረጡ ግጥሞችንም አቅርበዋል፡፡ በ110 ገጾች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ ለአገር ውስጥ በ30 ብር፣ ለውጭ በ9.99 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

   ወደ  አስኳላ ሲሰዱኝ የስደት ሕይወትን አሀዱ አልኩኝ። ከጎጆዬ ተነቅዬ ወደ አዲስ ግዛት በመጓዝ ከየኔታ እግር ስር ሆኜ ሀሁ ማለት ጀመርኩ። የኔታ ከነፍሴ ጋር የነበረችውን ቀጭን ገመድ ለመበጠስ ክርክሩን በማስፋት ጀመሩ።  የአቅማቸውን አበጃጅተውኝ ለቀጣይ የሙያ ጓዳቸው  አቀበሉኝ። በቅብብሎሽ ሲያገላብጡኝ ሲጠጋግኑኝ አዘገምኩ። ስመስል ሳስመስል እንድኖር ተፈረደብኝ። የወንዜ አድባር  ባበጀለኝ ሕግ እና ደንብ ስፈራ ስቸር ይኸው እንዳለሁ አለሁ። ትውልድ “ቀራጩ”፣ መምህሬ ይሄንን ትመስላለህ ብሎ ከፊት ለፊቴ የቁም መስታወት ደነገረብኝ:: እኔም ተጨብርብሬ ይሄንን እመስላለሁ ብዬ ደመደምኩ። እውን ይሄን እመስላለሁ?
በቤቴ በእናት ጓዳ እያለሁ የአላፊ አግዳሚውን አይን የምይዝ እምቦቃቅላ ነበርኩ። በእረኝነት ከመስክ ላይ ስቦርቅ የተመለከተ አንድ የጥበብ ሰው ፎልፏላ ለጋው የጨቅላ ገጽታዬን በአስደማሚ የጥበብ ሥራ በሸራ ላይ ወጥሮ ቀለም ረጭቶ አበጃጀኝ። ሀገር ምድሩ ይህንን ገጽታዬ ያለበትን ሸራ በየቤቱ አንጠለጠለው። በእኔ የጨቅላ ፎቶ የማይባረክ ሀገሬው አልነበረም። ይህ መሰሪ የጥበብ ሰው አሁን በግዞት ላይ ያለኝን ገጽታ በተለመደ የጥበብ ሥራ ውብ አድርጎ ቀረጸኝ። ከዓመታት በፊት ያበጃጀኝ ጨቅላው እረኛ እንደነበርኩ ሰዓሊው ልብ አላለም ነበር። ይሄኛውን ገጽታዬን ግን ደፍሮ የሚመለከትለት ጠፋ። የልጅነት እና “የአዋቂነት” (የግዞት) ገጽታዬን መሳ ለመሳ ሰቆሎ እያየ በተቃርኗቸው ተሳለቀ።
ሁለቱም ባለሙያዎች በየፊናቸው አበጃጅተው ያኖሩት ሰው ሆኜው አረፍኩ። መምህራኖቼ የመንፈስ ክሳቴን። ሰዓሊው በአካል መጠውለጌን። ከልጅነት እስከ እውቀት። ከየኔታ እስከ ኮሌጅ መበጠስ። በሁለት ሀዲድ ተጓዝኩ። የማይፈራው ፎልፏላው፣ ብሩሁ ሰብእና አሁን ከእዚህ የለም። ከእዚህ ያለው ሰብእና ሁለተኛው፣ ስደተኛው “አዋቂው” ነው፡፡ በኮሽታ ይደነብራል፤ ስንዝር ተራምዶ ኋላውን ይሰልላል፤ ስሜቱ በየአፍታው የሚጎዳ የስለት ልጅ ነው። በክርታስ ተከልሎ ቢኖር ግድ የማይለው፣ ጉስቁልናን የእጅ አምባሩ፣ ጌጡ የሚያደርግ ባተሌ ፍጡር ነው። ጠብ ያለሽ በዳቦ ምግባሩን ባልንጀራው ላይ ሳይቀር የሚያሳይ፣ ከሳር ከቅጠሉ ደም የተቃባ፣ የቃየል ምግባር ከላዩ ላይ የተደፈደፈበት ትልቁ፣ ስደተኛው ሰው ነው እዚህ ያለው።
ደግሞ እዚህ ሌላ ሰው አለ። አቤል። የበኽር ልጅ ነው። ድሮ የነበረ። ወደፊትም የሚኖር አልፋ እና ኦሜጋ። በእረኝነት በልጅነት እንደተያየን ነው። ከአይን የራቀ ከልብ ያልራቀ። በልብ የታተመ ዘላለማዊ ትስስር። ሃገሩ ሰማይ ወሰኑ አድማስ ነው። ጠጠር ላበደረ ወርቅ ይሰጣል። ልግስናው ከሃገሬው ደንብ ጋር አይገጥምም። የፍቅር እና የሀሴት ቤተመቅደስ ነው። የብርሃኑ ወጋገን ለእልፍ አዕላፍ ይተርፋል። ሰላምም ደስታም ከእዚሁ ከደጁ ነው የበቀሉት።
ልጅነቴ አቤል እና ስደተኛው ቃየል እሰጣ ገባ አላስቆም አላስቀምጥ አለኝ። አንተ ትብስ አንቺ ትብስ ተባብለው በአንድ ጣሪያ ስር መኖር የማይታሰብ ሆነ። ልጅነቴ አቤል በተመስጦ ነው የሚያረፋፍደው። ስደተኛው፣ “አዋቂው” ቃየል ይህንን ተመስጦ ከድፍረት ይቆጥረዋል። አቤል ግራውን ሲመታ ቀኙን ለዳግም ምት ያዘጋጃል። ለቃየል። ቃየል ቢወግር ቢወግር ክንዱ የማይዝል ሞገደኛ ነው። ማጀቱን የሞላው የንጹሀንን አንገት መበጠሺያ ቀስት ነው። ግፉን ለመጋት ቤት ለእግዚሀር ይላል። መካን አንጀቱ በአቤል በወላድ አንጀት ላይ ይጨክናል። የተመኘውን የሚያድነው ጦረኛው ቃየል ውስጤ ላይ አቆጥቁጦ ….አቁጥቁጦ….ውሎ አድሮ ወደ ደንነት ተለወጠ። የቃየልን ደን ለበሰኩኝ።
በቃየል ደን ውስጥ ሰላም እና ፍቅር ታዳኝ አውሬዎች ናቸው። የቃየል መስዋዕቶች ደም እረፍት እየነሳኝ ተቸገርኩኝ። ቃየል እና አቤል። ልጅነት እና ጉልምስና። የምስራች እና መርዶ። ፍትህ እና እድሎዎ። ንፉግነት እና ልግስና። ብጽህና እና እርኩሰት። ብህትና እና ግርግር። ሁለት እኔነቶች እንዴት ይኑሩ?
ከእጄ ላይ ነፍስ ሊያልፍ ነው። የንጹህ ነፍስ እንዳልሆነ እረዳለሁ። ደሙ ደመ ከልብ ሊሆን። ከላዬ ላይ ዱቄት እንደጠገበ ማዳበሪያ ሊራገፍ። ቁርጠኛ ውሳኔዬን እንደ ምጽአት ቀን ለዘመናት ተጠባበቀ። እርግጥ ነው ሀሞቴን ኮስተር አድርጌያለሁ። ወንድ ወንድ እየሸተትኩ ነው። ስደተኛውን ቃየል ጨለምለም ካለው ጎሬው አባብዬ ወደ አውላላ አውጥቼ ሞትን ጋትኩት።
ፍርደ ገምድል እንዳልሆኑክ ይገባኛል። “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሀዘንሽ ቅጥ ያጣ ከቤትሽ አልወጣ።” ጉንጭ አልፊ ስንኝ ሆነብኝ።
ዝምድናውም ቅርርቡም ይቅርብኝ ብዬ ቃየልን ገደልኩት። ፋኖ ተሰማራን በቃየል ላይ ተገበርኩት። ቃየል፣ ስደተኛው ሰብዕና ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አሸለበ። አሁን ያለው የድሮ ቤቴ ልጅነቴ፣ አቤል ነው።
 ዛሬ የቃየል የቀብር ስነ-ስርዓት የሚከበርበት ቀን ነው። የአብራኩን ክፋይ ያጣው ጀማው ፊቱ ጠይሟል። ሰማዩ አኩርፏል። የወንዜው ነዋሪ የአብራኩን ክፋይ በድኑን ሊሸኝ በነቂስ ነው የወጣው። እዚህም እዚያ ደረት ይደቃል።
እምባ ይንዠቀዠቃል። ተንዠቅዥቆ ተንዠቅዥ… መስኩን እንደ ጠል አውርዝቶታል። ስለ ቃየል ገድል አስለቃሿ ስንኞችን ትደረድራለች ፡-
አንበሳን ሲገድል
 ጎሽንም ሲገድል
  ወንድነት
  ሳይጓደል
 በቀን-ጎዶሎ
 ከአፈር ሊመሳሰል
ከእኔ በላይ ማወቋ ደንቆኛል። የአደባባይ ገበናን እንደታቀፍኩ ገባኝ። ሁሉም የሚያውቀው ጸሀይ የጠገበ ገበና። ገድለ ብዙው ቃየል ለኑዛዜ እንኳን የተውኩለት ቅጽበት አልነበረም። እንደው በድንገት ግጥም አለ።
ጀማውን ሳይሰናበት፣ ለበሽታው ሳይጫጫስለት የብኩን ሞትን ሞተ። ሀዘኑን ያከፋው ይህ ሳይሆን አይቀርም።
ወደ ተማሰው ጉድጓድ እየተቃረብን ሳለ ድንገት የዘነጋሁት ነገር እንዳለ ታወሰኝ። ለቃየል መቀበር፣ለጠንቀኛው ሰብዕና ማሸለብ ወሳኙ መከርቸሚያ የመጨረሻ ሚስማሮች አልተመቱም፡፡ ቃየልን በቃል ገድዬው ተግባሩን ዘንግቼው ኖሯል። ንጽሕናን በመሃላ በቃላት ጨዋታ ከውኜ፣ ቃየልን አዳፍኜው ኖሯል፡፡ የተሸከምኩትን ሳጥን በፍጥነት አወረድኩ። ሚስማሮቹን አውጥቼ ገርበብ ያለውን ሳጥን ልከረችመው ስንደረደር ሬሳው ድምጽ አሰማ። ለቀስተኛው በኦኦታ በእልልታ… በሽለላ የሀዘኑን አየር ገረሰሰው። አይኔን ማመን አልቻልኩም። ቃየል ሳጥኑን በርግዶ ጣቱን ወደ እኔ እየጠቆመ ተጠጋኝ፤
“ከደመኛዬ ጋር ምን ጉዳይ አላችሁ? ይህ አመለኛ ከብት እንዳይበጠብጣችሁ ፈጥናችሁ አብሩት” አለ ለለቀስተኛው፡፡
ቃየል እንደጨከንኩበት እርሱም በተራው ጨከነብኝ። ሁለት ወዶ አይሆንም። እኔም አቤልን፣ ልጅነቴን ይዤ እግሬ አውጭኝ ብዬ ጀማውን ተለየሁ።
በሽሽት፣ አይንን በመክደን ከአቤል ጣውንት ከቃየል ለጊዜው ነፃ ሆኜ ይሆናል…..ግን ግን….. ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ…..ካልፈጣጠምኩት……መልሶ ምርኮው የሚያደርገኝ ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 02 May 2015 12:35

የሰዓሊያን ጥግ

  ፎቶግራፍን አታነሳውም፤ ትፈጥረዋለህ እንጂ፡፡         ቶማስ ሜርቶን
ለማየት ስል ዓይኖቼን እጨፍናለሁ፡፡
ፖል ጋውጉይን
እንደ ስሜቶች ሁሉ ቀለማትም የህይወት ነፀብራቅ ናቸው፡፡     ጃኒሴ ግሊናዌይ
ቀለማትና እኔ አንድ ነን፡፡ ሰዓሊ ነኝ፡፡
ፖል ክሊ
ሰዓሊ ጥሩ ነገር የሚሰራው እየሰራ ያለውን የማያውቅ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
ኤድጋር ዴጋስ
የሰዓሊ ሥራ ሁልጊዜም ምስጢሩን ጥልቅ ማድረግ ነው፡፡
ፍራንሲስ ቤከን
ለመሳል ዓይኖችህን መጨፈንና ማዜም አለብህ፡፡
ፓብሎ ፒካሶ
በስዕልና በግጥም ሰስብዕና ሁሉም ነገር ነው፡
ገተ
ማንኛውም ጅል ስዕል መስራት ይችላል፤ ለመሸጥ ግን ብልህ ሰው ይፈልጋል፡፡
ሳሙኤል በትለር
መጀመሪያ ደንስ፤ በኋላ አስብ፡፡
ሳሙኤል ቤኬት
ነገሮችን የምስለው እንደማያቸው ሳይሆን እንደማስባቸው ነው፡፡     ፓብሎ ፒካሶ
ቀለማት የተፈጥሮ ፈገግታዎች ናቸው፡፡
ሊይግ ሃንት
ሰው ሁሉ ስዕልን ለመረዳት ይፈልጋል፡፡ ለምንድን ነው የአዕዋፋትን ዝማሬ የመረዳት ሙከራ የሌለው?
ፓብሎ ፒካሶ
የራሴ ስዕሎች ባለቤት አይደለሁም፤ ምክንያቱም የፒካሶ ኦሪጂናል ስዕል ብዙ ሺ ዶላሮች ያወጣል ይሄ ከአቅሜ በላይ የሆነ ቅንጦት ነው፡፡
ፓብሎ ፒካሶ

Published in ጥበብ