ታዋቂው ፈላስፋ ፕላቶ “የአንድ ሥራ ዋናውና ጠቃሚው አካል አጀማመሩ ነው፡፡” ይላል፡፡ በእርግጥ በየትኛውም የሥራ ፈርጅ መጀመር ከባድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ካቀዳቸው በርካታ አገራዊ ተግባራት መካከል አንዱ ባሕል ማዕከል ማቋቋሙ ነው፡፡
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባሕል ማዕከል ከተቋቋመ ሁለት ዓመታትን ያሳለፈ ሲሆን ዘንድሮ ከሚያዝያ 18 - 19 ቀን 2007 ዓ.ም 2ኛውን ሀገር አቀፍ የጥናትና የምርምር ሲምፖዚየም አካሂዷል፡፡ በሲምፖዚየሙም ለሀገርና ለሕዝብ በእጅጉ ጠቃሚ የሆኑ ጥናታዊ ጽሑፎችና ልዩ ልዩ ባሕላዊ ሥራዎች ቀርበውበታል፡፡ ጅማሮና ጀማሪነት የሚያስከትሉት ውጣ ውረዶች እንዳሉ ሆነው ዩኒቨርሲቲውና የባሕል ማዕከሉ ተቀናጅተው እያከናወኗቸው ያሉት ሥራዎች ተስፋ ያነገቡና ልብን የሚሞሉ ናቸው፡፡
በሲምፖዚየሙ የመጀመሪያ ቀን መርሐ ግብር፣ ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ጋር ሁለገብ ተግባራትን ለማካሄድ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ሥነ - ሥርዓቶች ተከናውነዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከአንጋፋው የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት መወሰኑ ለሀገራችን የሥነ - ጽሑፍ እድገት መስፋፋት ያለውን ቁርጠኛነት በውል የሚያስረግጥ እርምጃ ነው፡፡ በዕለቱ የታዩት ኪነታዊ እንቅስቃሴዎችም የባሕል ማዕከሉ የሰሜን ሸዋን የሙዚቃና ልዩ ልዩ ኪነታዊ እሴቶች ለማስተዋወቅ አልሞ እየሠራ መሆኑን ያመለክታል፡፡
በሁለተኛው ቀን የሲምፖዚየሙ መርሐ ግብር ውሎ፣ በርካታ ጥናታዊና የምርምር ወረቀቶች ቀርበዋል፡፡ አብዛኞቹ ጥናቶች እጅግ ጠቃሚና በውል የታሰበባቸው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዕለቱ አሥራ አንድ ጥናታዊ ወረቀቶች /ጽሑፎች/ የቀረቡ ሲሆን ስድስቱ በባሕልና ቱሪዝም፣ አምስቱ ደግሞ በሥነ ጽሑፍ ዙሪያ ያጠነጥናሉ፡፡ ከነዚህ ሥራዎች መካከል “የባሕል ኢንዱስትሪ ጽንሰ ሃሳብ ዳሰሳ”፣ “ባሕልና ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን)”፣ “የመካከለኛው ዘመን ሥነ - ጽሑፍ አጀማመርና እድገት (በኢትዮጵያ)”፣ “የሰብአዊነት የትረካ ሥልት በአፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕልና በበዓሉ ግርማ የቀይ ኮከብ ጥሪ መጽሐፍ ውስጥ” እና ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ የኢትዮጵያን ታሪክ ከማጥናት አንፃር ያለው ፋይዳ” የሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረትን የሳቡ ነበሩ፡፡ ሌሎቹ ጥናታዊ ወረቀቶችም ቢሆኑ ጠቃሚና ሠፊ ተሞክሮዎች የተገበየባቸው ናቸው፡፡
በቀረቡት ጽሑፎች በተለይ ሉላዊነት /ግሎባላይዜሽን/ በወቅቱ የአገራችን ነባር ባሕላዊ መዋቅር ላይ እያስከተለ ያለውን የማፈራረስ ሂደት በአጽንኦት ለመመልከት አስችሏል፡፡ ጉዳዩ በለሆሳስ የሚታለፍ ሳይሆን ሁሉም ወገን ተረባርቦ የሀገርን ነባር ጠቃሚ የባሕል እሴት በመታደግ ማዘመንና ማሳደግ እንደሚገባ በአንክሮ የሚታይ ነው፡፡ በመጤ ባሕል መወረርን ተቀብሎ እጅ ከመስጠት ይልቅ ጠቃሚውን ብቻ በመምረጥ ከራስ በቀል ወይም ነባር ባሕል ጋር አዛምዶ ለመሄድ የመታተሪያ ጊዜው አሁን እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ በዚህ ረገድ እድገት የሚፋጠነው በባሕል ኢንዱስትሪው ውስጥ በራስ የመተማመንና የፈጠራ ዕውቀት እየተጠናከረ ሲሄድ መሆኑን የቀረቡት ጥናቶች በሚገባ አስምረውበታል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በፌደራል ደረጃ ከተመሠረቱ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን በተጓዘባቸው አጭር ጊዜያት ውስጥ ከፍተኛ እመርታን ሊያጐናጽፉት የሚችሉ ሥራዎችን እያካሄደ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የውስጥ አደረጃደቱን በየጊዜው እያሳደገ ከመሆኑም በላይ በቅርብና በርቀት ካለው ማህበረሰብ ጋር በመተሳሰር ችግር ፈች የሆኑ የምርምርና የሥርፀት ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ከሌሎችም ኃላፊዎች ገለፃ ለመረዳት ተችሏል። በመሆኑም ከባሕልና ቱሪዝም ተቋሞችና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር በመተባበር የታሪክና የቱሪዝም መስህቦችን በማጥናትና በመለየት፣ ለተወሰኑ የአካባቢው ሀብቶች ቋሚ ምልክት (ብራንድ) እንዲሠጣቸው በጥናት በማገዝ፣ እንደየግዕዝ ቋንቋ ወዳጆችና ሌሎችንም ለዩኒቨርሲቲው አጋዥ ማህበራትን በመመሥረትና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ጋር በመተጋገዝ የመሥራትን መንፈስና ተግባር እያዳበረ ይገኛል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ እየተገነቡ ያሉት ዘመናዊ የቤተ መጻሕፍትና የሁለገብ አዳራሽ ሕንፃዎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ትልቅ የአቅም ግንባታ ግብአት እንደሚሆኑ አያጠራጥርም፡፡
ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ሙያ ባለቤት የሆኑ ምሑራንና የሕዝብ ወኪሎች በታላላቅ ምርምርና ሥርፀትም ሆነ በሌሎቹ ሥራዎቹ በቅርብ ይታገዝ ዘንድ የዩኒቨርሲቲው የወዳጆች መማክርት ለመመሥረት እየተዘጋጀ ነው፡፡ አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎች በቅርቡ በሚደረግ ሠፊ ጉባዔ የሚቀርቡ ሲሆን የጅሩ ሠንጋ፣ የመንዝ ቅቤ፣ የደብረ ሲና ቆሎና የምንጃር ጤፍ የቋሚ ምልክት (ብራንድ) እንዲኖራቸው በተጠናው መሠረት ውጤቱ ይፋ ይደረጋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለሥንፍና ቦታ ሳይሰጥ በያዘው ሰፊ እንቅስቃሴ እየገሠገሠ በሄደ ቁጥር እጅግ አስደማሚ ውጤቶች ለመጨበጥ ጊዜ የሚወስድበት አይመስለኝም፡፡ ታላቁ የፈረንሳይ ፈላስፋና ደራሲ ቮልቴር፤ “ሥራ ከሦስት ታላላቅ እኩይ ተግባራት ይጠብቀናል። እነርሱም ስንፍና፣ ንቅዘትና ድህነት ናቸው፡፡” ይላል፡፡ በእርግጥም በሥራ ተጠምዶ ውጤቱን እንደመጨበጥ አኩሪ ተግባር ምን ይኖራል?
ዩኒቨርሲቲው በተለይም በመሬት መጣበብና መምከን ሳቢያ እየተፈናቀለ ልቡ ወደ ስደት ያቆበቆበውን የአካባቢውን ወጣት በሥራ ለመጥመድ የሚያስችሉ የምርምር ተግባራትን በአፋጣኝ እንደሚጀምር ጥርጥር የለኝም፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው በሚያስደንቅ የእድገት ሂደት ላይ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች በመስፋፋት ላይ ናቸው፡፡ ይህ በአንድ በኩል ወደ ኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚ የመሸጋገራችንን እውነትና በሀብት፣ በሥራ ፈጣሪነትና ሥልጣኔን በማምጣት የማይተካ ሚና ሲኖረው፤ በሌላ በኩል ግን ተያይዘው የሚከሰቱ (የሚመጡ) እንደ አየር ብክለት፣ አካባቢያዊ ንጽሕና ጉድለትና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮች መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለችግሮቹ የመፍትሔ ጥናትና ምርምር የሚያደርገውን ጐራ ለመምራት ከወዲሁ አቅሙን ማሳደግ ይጠበቅበታል፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባሕል ማዕከል፣ በዩኒቨርሲቲው ጥላ ሥር ይበልጥ በመጠናከር በዘንድሮው ሲምፖዚየም ማጠቃለያ ላይ ከተሳታፊዎች የተሰጡትን አስተያየቶች በመቀበልና ጠቃሚዎቹን በተግባር ላይ በማዋል በቀጣይ ሥራዎቹ ይበልጥ ጐልብቶ ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ ውጤቶችን እንደሚያስጨብጥ ጽኑ እምነት አለኝ፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 02 May 2015 12:22

የየአገሩ አባባል

ጥበብ አልባ ዕውቀት በአሸዋ ላይ እንዳለ ውሃ ነው፡፡
የጊኒያውያን አባባል
ሞኝ ያወራል፤ ብልህ ያደምጣል፡፡
የኢትዮጵያውያን አባባል
ጥበብ በአንድ ጀንበር አይመጣም፡፡
የሶማሊያውን አባባል
በቀውስ ሰዓት ብልህ ድልድይ ሲገነባ፣ ሞኝ ግድብ ይገነባል፡፡
የናይጄሪያውያን አባባል
በኩራት ከተሞላህ ለጥበብ ቦታ የለህም፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
ብልህ ሰው ሁልጊዜ መላ አያጣም፡፡
የታንዛንያውያን አባባል
ማንም ብልህ ሆኖ አልተወለደም፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
ትልቅ ወንበር ንጉስ አያደርግም፡፡
የሱዳናውያን አባባል
የአንበጣዎች ጠብ ለቁራ ፌሽታው ነው፡፡
የሌሴቶ አባባል
ደጋግሞ በመሞከር ጦጣ ከዛፍ መዝለል ትማራለች፡፡
የቡጋንዳ አባባል
ምክር እንግዳ ነው፤ የሚቀበለው ካገኘ ሌቱን ያድራል፡፡ ያለበለዚያ የዚያኑ ዕለት ይመለሰል፡፡
የማላጋሲ አባባል
መጓዝ መማር ነው፡፡
የኬንያውያን አባባል
ባለሙያዎች ባሉበት የተማሪዎች እጥረት አይኖርም፡፡
የስዋሂሊ አባባል
ወተትና ማር ቀለማቸው ይለያያል፤ ነገር ግን አንድ ቤት ተጋርተው በሰላም  ይኖራሉ፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
መግባባት ሳይኖር ሰላም ሊኖር አይችልም፡፡
የሴኔጋሎች አባባል
እየመራሁ ነው ብሎ የሚያስብና ተከታይ የሌለው ሰው የእግር ጉዞ እያደረገ ነው፡፡
የማላዊያኖች አባባል

Published in ጥበብ

 በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) ቴሌቪዥን “የጆርዳና ኩሽና ሾው”    አዘጋጅ ጆርዳና ከብዶም የተፃፈው “የጆርዳና የምግብ አዘገጃጀት” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ለገበያ ቀርቦ እየተነበበ ይገኛል፡፡ መፅሐፉ ከመቶ በላይ የውጭ ምግቦች አዘገጃጀትን የያዘ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን ከተለመደው የአመጋገብ ስርዓታቸው ወጣ ብለው እንደ ፓስታ፣ ፒዛ ያሉ የውጭ ምግቦችን በኩሽናቸው በቀላሉ አዘጋጅተው መመገብ እንዲችሉ ያግዛል ተብሏል፡፡ በኢቢኤስ ቲቪ “ጆርዳና ኩሽና ሾው” እውቅናን ያተረፈችው ባለሙያዋ፤ቦሌ ሩዋንዳ ኤምባሲ አካባቢ “ጆርዳናስ ኪችን ሬስቶራንት” የተሰኘ ምግብ ቤት ከፍታ የውጭ አገር ምግቦችን እያሰናዳች እንደምትሸጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) ቴሌቪዥን “የጆርዳና ኩሽና ሾው”    አዘጋጅ ጆርዳና ከብዶም የተፃፈው “የጆርዳና የምግብ አዘገጃጀት” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ለገበያ ቀርቦ እየተነበበ ይገኛል፡፡ መፅሐፉ ከመቶ በላይ የውጭ ምግቦች አዘገጃጀትን የያዘ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን ከተለመደው የአመጋገብ ስርዓታቸው ወጣ ብለው እንደ ፓስታ፣ ፒዛ ያሉ የውጭ ምግቦችን በኩሽናቸው በቀላሉ አዘጋጅተው መመገብ እንዲችሉ ያግዛል ተብሏል፡፡ በኢቢኤስ ቲቪ “ጆርዳና ኩሽና ሾው” እውቅናን ያተረፈችው ባለሙያዋ፤ቦሌ ሩዋንዳ ኤምባሲ አካባቢ “ጆርዳናስ ኪችን ሬስቶራንት” የተሰኘ ምግብ ቤት ከፍታ የውጭ አገር ምግቦችን እያሰናዳች እንደምትሸጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ጥበብ

ማልድ የትምህርት ድጋፍ ኃ.የተ.የግ.ማ ባቀራረቡ የተለየ የልጆችን የንባብን ባህል የሚያዳብር፣ ከመጽሐፍ ጋር የተያያዘ የወላጆች ቀን “Book and fun Kids day” /የህፃናት የንባብና የትምህርታዊ ጨዋታ ቀን/ የፊታችን ማክሰኞ በትሮፒካል ጋርደን መናፈሻ ከ4-11 ሰዓት ድረስ ማዘጋጀቱን ገለፁ፡፡
ከ4-14 ዓመት ላሉ ልጆች በተዘጋጀው በዚህ የልጆች ቀን፤ ወላጆች አስተማሪዎች እንዲሁም ትላልቆች ለልጆች መጽሐፍት ያነባሉ፡፡ ጸሐፊያን በዚሁ ቀን መጽሐፍ የማሳተምን ሂደት ለልጆች ያስረዳሉ፣ የተለያዩ ጨዋታዎችም ይኖራሉ፡፡ ማልድ በ21ኛው ክ/ዘመን ልጆች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ እንደሚገባቸው ይመክራል ተብሏል፡፡
ማልድ የትምህርት ድጋፍ ሰጪ አስተማሪዎችን በማሰልጠን፣ እንዲሁም ልጆችን ለክፍለዘመኑ ብቁ እንዲሆኑ የሚያግዙ በጥበብና በፈጠራ የተሞሉ ስልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃል፡፡

 የዋይት ሃውስ ባለስልጣናት ለሳምንታት በየዕለቱ መክረዋል

   ለጊዜው ማንነታቸው በውል ያልታወቀ የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ኢሜይል በህገ-ወጥ መንገድ ሰብረው በመግባት፣ መረጃዎችን ማግኘት እንደቻሉ መረጋገጡን ስካይ ኒውስ ባለፈው ሰኞ ዘገበ፡፡
የዋይትሃውስ የደህንነት ሃላፊዎች ቻይናውያን አልያም ሩስያውያን ሳይሆኑ ሲሉ የጠረጠሯቸው እነዚህ የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች፣ የይለፍ ቁልፉን ሰብረው በመግባት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለሌሎች ሰዎችና ድርጅቶች የላኳቸውንና ከሌሎች የተላኩላቸውን የኢሜል መልእክቶች ማግኜት መቻላቸው ተረጋግጧል፡፡ድርጊቱ የተፈጸመው ከሳምንታት በፊት ቢሆንም፣ የዋይት ሃውስ ባለስልጣናት ጉዳዩን ሸፋፍነውት እንደቆዩ የጠቆመው ዘገባው፣የአጭበርባሪዎቹ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን የሚያመለክተው ባለስልጣናቱ ላለፉት ሳምንታት በየዕለቱ እየተሰበሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ ሲመክሩ መቆየታቸው ነው ብሏል ዘገባው፡
ሩስያውያን የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች የኦባማን የኢሜል መልዕክቶች ለማግኘት የቻሉት፣ ባለፈው አመት በዋይት ሃውስ የሴኪውሪቲ ሲስተም ላይ በደረሰው ቀውስ ያገኙትን ክፍተት በመጠቀም ነው ተብሎ እንደሚገመት የገለጸው ዘገባው፣ ይሄም ሆኖ ግን አጭበርባሪዎቹ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለትን የኦባማ  የብላክቤሪ ስልክ መልዕክቶች ማግኘት እንዳልቻሉ አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

- ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው አልተሳተፉም
- ምዕራባውያን አገራት ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ አይደለም ብለዋል

 ዋና ዋናዎቹ የሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነጻና ፍትሃዊ አይሆንም በሚል ራሳቸውን ባገለሉበት የአገሪቱ ምርጫ የተወዳደሩት ፕሬዚዳንት ኡመር ሃሰን አልበሽር፤ 94.5 በመቶ ድምጽ በማግኘት በቀጣይም አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ መመረጣቸውን ቢቢሲ ዘገበ።የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ ሙክታር አል አሳም ባለፈው ሰኞ ከካርቱም በሰጡት መግለጫ፣ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት አልበሽር፤ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ያስታወቁ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በበኩሉ፤ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት 13.3 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ድምጽ የሰጡት አንድ ሶስተኛ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ አልበሽር በዘንድሮው የሱዳን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይህ ነው የሚባል ፉክክር እንዳልገጠማቸው የዘገበው ዘጋርዲያን በበኩሉ፣ ከተፎካካሪዎች መካከል የተሻለ ድምጽ ያገኙት ፌደራል ትሩዝ ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት ፋደል አልሳይድ ሹያብ መሆናቸውንና ያገኙት ድምጽም 1.43 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውቋል።ከሚያዝያ 5 ቀን ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በመላ አገሪቱ በተቋቋሙ 11 ሺህ የድምጽ ጣቢያዎች በተከናወነው የድምጽ አሰጣጥ ስነስርአት ላይ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ድምጽ አለመስጠታቸውንና ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው በተፎካካሪነት የቀረቡት 15 እምብዛም እውቅና የሌላቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎች ብቻ እንደነበሩም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ኖርዌይን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገራት፣ ላለፉት 25 አመታት ሱዳንን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አልበሽር፤ በከፍተኛ ድምጽ ያሸነፉበትንና ባለፈው ሰኞ የተከናወነውን የአገሪቱ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ነጻና ፍትሃዊ አይደለም፣ እውቅና አንሰጠውም ሲሉ የተቹት ሲሆን፣ የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂፒንግ በበኩላቸው፤ ለአልበሽር የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ልከዋል፡፡
ስቲስ ኤንድ ኢኳሊቲ ሙቭመንት የተባለው የአገሪቱ አማጺ ቡድን ባለፈው እሁድ በደቡብ ዳርፉር አካባቢ በሱዳን መንግስት ጦር ላይ በከፈተው ወታደራዊ ጥቃት የጦር ካምፕ ማውደሙንና የጦር መሳሪያዎችን መማረኩን ያስታወቀ ሲሆን፣ የአገሪቱ የጦር ሃይል በበኩሉ አማጽያኑ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ባደረገው ድብደባ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን አስታውቋል፡፡ በአየር ድብደባው 16 ሲቪል ዜጎች መሞታቸውንና ከ11 በላይ የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን የዘገበው አይቢታይምስ ነው፡፡
በዳርፉር ግጭት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ የቀረበባቸውና የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው የ71 አመቱ አልበሽር፣ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ሲሉ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡
ፕሬዚዳንት አልበሽር እ.ኤ.አ በ1989 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ አገሪቱን እየመሩ ሲሆን ሱዳንን ለረጅም ጊዜ በመምራት ቀዳሚው ሰው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የባሬቶ ስንብት
ለሁለት ወራት ስፖርት ቤተሰቡን ውዥንብር ውስጥ ከቶ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ቆይታ ባለፈው ሳምንት  መቋጫውን አግኝቷል፡፡ ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ባለፈው ማክሰኞ ወደ ትውልድ አገራቸው ከማምራታቸው በፊት የስንብት መግለጫቸውን ሰጥተው ነበር፡፡በትውልድ ህንዳዊ በዜግነት ፖርቹጋላዊ የሆኑት አሰልጣኙ  በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ለ10ወራት አገልግለዋል፡፡ ሰውነት ቢሻውን  ተክተው ስራቸውን ከጀመሩ በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እና ሌሎች የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ 19 ግጥሚያዎችን አከናውነው በ11ዱ ተሸንፈዋል፤ በአራቱ አቻ ሲወጡ እንዲሁም አራቱን ድል አድርገዋል፡፡ ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ ስምምነት መለያየታቸውን ለማመልከት በተዘጋጀው የስንብት  መግለጫቸው ላይ ሲናገሩ ‹‹በስንብቱ ሁለት ዓይነት ስሜቶች ተፈራርቀውብኛል፡፡ ጥሩው ስሜት ወደ ቤተሰቤ እና ሀገሬ መመለሴ ሲሆን መጥፎው  ደግሞ ከጥሩው የኢትዮጵያ ህዝብ መለያየቴ ነው፡፡ ኢትዮጵያን መቼም አልረሳትም ህዝቧ እግር ኳስን ይወዳል በተለይም ሀገሪቷ እንደ ቤት እንድትሰማኝ ላደረጉት በየስፍራው የደገፉኝን አመሰግናለሁ፡፡ ወደ ትግራይም ደብረዘይትም አዳማም በሄድኩባቸው ሁሉ ላየሁት ነገር ተደስቻለሁ›› ብለዋል፡፡ ለ10 ወራት በቆዩበት ሃላፊነት በተለይ ሶስት ኢትዮጵያዊ  አሰልጣኞች ገብረመድህን ሀይሌ፤ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እና ጳውሎስ ጌታቸው  ለሰጧቸው እገዛ ምስጋናቸውን የገለፁት ባሬቶ፤ ከፌዴሬሽን በኩል የፅህፈት ቤት ሀላፊውን አቶ ዘሪሁንን እንዲሁም ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ ፤ አብርሃም ተክለሀይማኖትን እና የተቋሙ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ተክለወይኒ አሰፋን ጭምር ላደረጉላቸው ቅን ትብብር ልባዊ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡ በስንብት መግለጫቸው ለመገናኛ ብዙሃናት ልዩ መልዕክት ያስተላለፉት ማርያኖ ባሬቶ፤ ለአገር ውስጥ የእግር ኳስ ውድድሮች በቂ ትኩረት መሰጠት እንዳለባቸው ፤ በሊጉ ታዳጊዎች እና ብቃት ያላቸው ተጫዋቾችንን ለማየት ጫና በመፍጠር መስራት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡
የዮሃንስ ቅጥር
ከማርያኖ ባሬቶ ስንብት በኋላ የኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዮሐንስ ሳህሌን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ እንዲሰራ የሾመው  አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ ከብሄራዊ ከቴክኒክና ልማት እንዲሁም ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተውጣጣ ኮሚቴ በማቋቋም ምርጫውን በፍጥነት በማከናወን አቅዶ ነበር፡፡
በብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ምርጫው በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋና አሰልጣኞች እድል የሰጠው ፌደሬሽኑ ባዘጋጀው የመምረጫ መስፈርት  የሁሉንም ብቃትና ደረጃ በዝርዝር በማየት አራት ተወዳዳሪዎችን በኮሚቴው አማካኝነት ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለይቶ አቅርቧል፡፡ አሰልጣኞቹ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ያላቸው ውጤት እና የትምህርት ደረጃቸውን ሲያወዳድርም ከአራቱ አሰልጣኞች ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም እና ፋሲል ተካልኝ የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ሲያገኙ አዲሱ የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ለመሾም የበቃው ዮሐንስ ሳህሌ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት የደደቢት ክለብ ዋና አሰልጣኝ ለሆነው ዮሃንስ  ሳህሌ አስፈላጊውን የቅጥር ስርዓት በፍጥነት በማጠናቀቅ በቀጣይ ሳምንት ስራውን እንደሚጀምር ፌደሬሽኑ ገልጿል፡፡
የዮሃንስ ልምድ፤ ደሞዛቸው
በእግር ኳስ ስልጠና ትምህርታቸው የኢንስትራክተርነት ማእረግ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በተጫዋችነት ዘመናቸው ለራስ ሆቴል፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጫወት አሳልፈዋል፡፡ በ1975 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ዋንጫን ከጊዮርጊስ ጋር ማሸነፍም ችለዋል፡፡ በአሜሪካም ለተለያዩ ክለቦች ተጫውተው ያሳለፉት ዮሃንስ ሳህሌ፤ በአሰልጣኝነት ህይወታቸው በአሜሪካ የተለያዩ የኮሌጅ ክለቦችን ለማሰልጠንም የቻሉ ነበሩ፡፡ ከአሜሪካ መልስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተርም የነበሩ ሲሆን ከዚያ በኋላ የሃረር ቢራ ክለብ ስራ አስኪያጅ ሆነው ከሰሩ በኋላ በ2006 አ.ም የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል፡፡ አስቀድመው የደደቢት እግርኳስ ክለብን በቴክኒካል ዳይሬክተርነት ካገለገሉም በኋላ የክለቡ አሰልጣኝ ሆነው በመቀጠር ያለፉትን ወራት ቡድኑን በሃላፊነት መርተዋል፡፡ ከኢትዮጵያዊነታቸው በተጨማሪም የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው አሰልጣኙ እግር ኳስን በአሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሆላንድ እና ጀርመን በመማር የስልጠና ብቃታቸውን አሳድገዋል፡፡ አሰልጣኙ በተለይ በስፖርት ቤተሰቡ የሚታወቁት ከአሜሪካ የረጅም ዘመን ቆይታቸው ከተመለሱ በኋላ በ1990ዎቹ አጋማሽ ለአሰልጣኞች በሰጧቸው የአሰልጣኝነት ስልጠና ኮርሶች ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድን  ደረጃ የማሰልጠን ልምድ ባይኖራቸውም በዩናይትድ ስቴትስ የወጣቶች አካዳሚዎች ውስጥ መስራታቸውና የማስተዳደር ክህሎት በመያዛቸው  ቡድኑን ወደፊት ሊያራምዱት ይችላሉ ተብሏል፡፡
የ59 ዓመቱ ማርያኖ ባሬቶ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነታቸው የተጣራ ወርሃዊ ደሞዛቸው 18ሺ ዶላር ሲሆን ሌሎች ወጭዎችን ሳይጨመር በ10 ወራት ቆይታቸው  በደሞዝ ብቻ 180ሺ ዶላር አግኝተዋል፡፡ ኮንትራታቸው ሲቋረጥ ደግሞ የ3 ወራት ደሞዛቸው 54ሺ ዶላር በፌደሬሽኑ ተከፍሏቸዋል፡፡ ማርያኖ ባሬቶ በአጠቃላይ በደሞዝ ብቻ ፌደሬሽኑን ያስወጡት 234 ሺ ዶላር ነበር፡፡ በአንፃሩ የአሁኑ የብሄራዊ ቡድን ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቢያንስ ከ80ሺህ-100ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ይከፈላቸዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ከማርያኖ ባሬቶ በፊት የነበሩት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ደሞዛቸው 60ሺ ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ስለ ኢትዮጵያዊ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ቅጥር የጀመረው ከ1946 ጀምሮ እንደሆነ ታዋቂው የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ ባንድ ወቅት አቅርቦት በነበረው ጥናታዊ ፅሁፍ ተመልክቷል፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽን ከመጀመሪያው ተቀጣሪ የውጭ አሰልጣኝ ኦስትሪያዊው ጆርጅ ብራውን እስከ ማርያኖ ባሬቶ ድረስ 39 የውጭ አሰልጣኝ በመቅጠር ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ መሞከሩን በፅሁፉ ያመለከተው ገነነ መኩርያ፤ ከዚህ ጋር አያይዞ ባቀረበው ትንታኔ በዋና ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት ከዮሃንስ ሳህሌ በፊት 41 ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች በሃላፊነቱ ማለፋቸውን ሲዘረዝር  አዳሙ አለሙ፤ጸሀዬ ባህረ፤ሉቻኖ ቫሳሎ፤ታደሰ ወልዳረጋይ፤ሽፈራው አጎናፍር፤፤መንግስቱ ወርቁ፤ዶክተር ተስፋዬ ጥላሁን፤አስራት ሀይሌ፤ስዩም አባተ፤ጌታሁን ገብረጊዮርጊስ፤ ካሳሁን ተካ አዳነ ሀይለየሱስ፤ጸጋዬ ደስታ፤ሰውነት ቢሻው ፤መኩሪያ አሸብር........ እና ሌሎችም መሆናቸውን ጠቃቅሷል፡፡ የእግር ኳስ ጋዜጠኛው ገነነ መኩርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ከሰሩት 41 ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች መካከል 13ቱ 2 እና ከሁለት ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ተቀጥረው መስራታቸውን አብራርቷል፡፡  ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት የተሾሙ 42ኛ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ናቸው ማለት ነው፡፡
የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በአፍሪካ እግር ኳስ ከፍተኛ ክብር ቦታ ያላቸው ይድነቃቸው ተሰማ ሲሆኑ በ1962 እ.ኤ.አ ለአንድ አመት በሃላፊነቱ ቆይተዋል፡፡ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ለብሄራዊ ቡድኑ መቀጠር የቻለው ከ20 ዓመት በኋላ ሲሆን ሃላፊነቱን ሊያገኙ የበቁት በተጨዋችነት በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ ብቸኛውን የሻምፒዮንነት ክብር እንድታገኝ ያስቻሉት ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ ነበሩ፡፡ ከ1982 እስከ 87 እኤአ ድረስ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በሃላፊነት የሰሩት ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ ለአምስት አመታት በሃላፊነቱ መቆየት በተከታታይ ዓመታት ለረጅም ጊዜ የቆዩ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ ስዩም አባተ፤ ካሳሁን ተካ እያንዳንዳቸው ለሶስት ጊዜያት በተለያዩ ጊዜያት፤ ሰውነት ቢሻው ለሶስት አመት በተከታታይ፤ አስራት ሃይሌ ለሁለት ጊዜያት በተለያየ ቅጥር ብሄራዊ ቡድኑን በሃላፊነት በመምራታቸው ታሪክ ያስታውሳቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተሳተፈባቸው 10 የአፍሪካ ዋንጫዎች ሁለት ጊዜ ብቻ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች በሃላፊነት ሰርተዋል፡፡ እነሱም መንግስቱ ወርቁ እና ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች ውጤታማው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ በእርግጥ አሁን 63 ዓመት የሞላቸው ሰውነት ቢሻው ለሁለት ጊዜያት ብሄራዊ ቡድኑ ይዘው ለአምስት አመታት ሰርተዋል፡፡ የሴካፋ ዋንጫን አግኝተዋል፤ ከ31 ዓመታት ቆይታ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ አብቅተዋል፡፡መንግስቱ ወርቁ ደግሞ በ5 አመታት የስራ ዘመናቸው በ1982 ብሄራዊ ቡድኑን ለ10ኛው አፍሪካ ዋንጫ ይዘው የቀረቡ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ የሚጠቀሱት አሰልጣኝ አስራት ሃይሌ ሲሆኑ በሶስት የተለያዩ ጊዜያት ብሄራዊ ቡድኑን በሃላፊነት ይዘው ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎችንም አግኝተዋል፡፡
ዮሃንስ የሚፈተኑባቸው ማጣርያዎችና ተቀናቃኞቻቸው
የኢትዮጵያ  ብሄራዊ  ቡድን ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በቻን 2016 እና በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ  የማጣርያ ውድድሮች የሚሳተፍ ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ በ2018 እኤአ ለሚካሄደው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የጥሎ ማለፍ ማጣርያዎች ናቸው፡፡ አዲሱ የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ  ዮሃንስ ሳህሌ  በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የሚሰጣቸው የኮንትራት ቆይታ ከላይ በተጠቀሱት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚኖራቸውን ስኬት በመንተራስ የሚለካ ይሆናል፡፡ ለዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የመጀመርያው የነጥብ ጨዋታቸው ከወር በኋላ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሌሶቶን የሚያስተናግዱበት ይሆናል፡፡ ከዚያም በሁለተኛ ጨዋታቸው በ2016 የቻን ማጣርያ ኬንያን በሜዳቸው ከዚያም  ከሶስት ሳምንታት በኋላ ከሜዳቸው ውጭ የሚገጥሙበት ነው፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ዞን በ2018 በራሽያ አዘጋጅነት ለሚደረገው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ማጣርያዎቹ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም ላይ ይጀመራሉ፡፡ 52 አገራት  በ9 ወራት ውስጥ በአራት ዙር የማጣርያ ምእራፎች ለሚገቡበት ፉክክር የመጀመርያው የቅድመ ማጣርያ ድልድል ከወር በኋላ በሩስያ የሚወጣ ሲሆን ኢትዮጵያ በሶስት ዙር ቅድመ ማጣርያዎች በጥሎማለፍ ከሶስት የአፍሪካ ቡድኖች ጋር የምትገናኝ ይሆናል፡፡
በ2017 እኤአ ጋቦን በምታዘጋጀው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሚሳተፍበት የምድብ ማጣርያ በምድብ 10 ከአልጄርያ፤ ከሌሶቶ እና ከሲሸልስ ጋር መደልደሉ ይታወቃል፡፡ በዚሁ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ውድድር ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ተቀናቃኝ ሆነው ከሚቀርቡት አሰልጣኞች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ፈረንሳዊው ክርስትያን ጉርኩፍ ናቸው፡፡
በ2017 በጋቦን በሚስተናገደው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በሚደረገው ማጣርያ ምንም የምንዘናጋበት ሁኔታ የለም በማለት ባለፈው ሰሞን የተናገሩት ክርስትያን ጉርኩፍ፤ የምድብ 10 ትንቅንቅ በእኛ እና በኢትዮጵያ ይሆናልም ሲሉ ተናግረው፤ ግን ሲሸልስ እና ሌሶቶንም እንደማይናቁ አስገንዝበዋል፡፡ በማጣርያው ከሚያደርጓቸው ግጥሚያዎች ከኢትዮጵያ ጋር በአዲስ አበባ የሚያደርጉትን ከባድ ጨዋታ እንደሆነ በመጥቀስም ምንም አይነት ስህተት መፍጠር የለብንም ሲሉ ለቡድናቸው አባላት አሳስበዋል፡፡ የአልጄርያ ቡድን ለማጣርያው የሚያደርገውን ዝግጅት ከሁለት ሳምንት በኋላ ካምፕ በመግባት ይጀመራል፡፡በፈረንሳዊው የቡድኑ አሰልጣኝ ጉርኩፍ ስር ከ10 በላይ ባለሙያዎች አብረው እንደሚሰሩ መጥቀስ ለንፅፅር ይሆናል፡፡ አሰልጣኙ የአልጄርያን ቡድን በሃላፊነት የሚመሩት በስራቸው  ሁለት ምክትል አሰልጣኞች ከአልጄርያ ፤ አንድ ስራ አስኪያጅ ከአልጄርያ፤ ሁለት የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ከአልጄርያ እና ከፈረንሳይ፤ ሁለት የአካል ብቃት አሰልጣኞች ከፈረንሳይ እንዲሁም ሁለት ዶክተሮች ከአልጄርያ ተመድበውላቸው ነው፡፡
 በሌላ በኩል በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው ለኢትዮጵያው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ተቀናቃኝ ሆነው የሚቀርቡት የሲሸልስ እና የሌሶቶ አሰልጣኞች ሁለቱም በአገራቸው በምርጥ ተጨዋችነት ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡ የሲሸልስ እና የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድኖች በእግር ኳስ ደረጃቸው ከኢትዮጵያ በታች በመሆናቸው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በሁለቱ ተቀናቃኞቻቸው ላይ ብልጫ ለመውሰድ የሚችሉበትን እድል ያመለክታል፡፡ የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ኡሊርች ማቲሆልት ይባላሉ፡፡ ኡልሪች በሲሸልስ  እግር ኳስ ብቸኛው ፕሮፈሽናል ተጨዋች በመሆን የሚጠቀሱ ባለታሪክ ሲሆኑ  በ1991 እና በ2008 እኤአ የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ከሰሩ በኋላ በ2014 ለሶስተኛ ጊዜ ሃላፊነቱን በመረከብ እየሰሩ ናቸው፡፡ ከዚያ በፊት በ2010 እኤአ የሲሸልስ እግር ኳስ ፌደሬሽን የእግር ኳስ ዲያሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በገቡበት የምድብ ማጣርያ ዙርያ ኡሊርች ማቲ ሆልት አስተያየት ሲሰጡ የምንመጥነው ሌሶቶን ነው ካሉ በኋላ፤ የኢትዮጵያ ቡድን እየጠነከረ የመጣ እና የሚበልጠን ነው ብለው አልጄርያ ግን ከአቅማችን በላይ ናት በማለት ተናግረዋል፡፡ በህንድ ውቅያኖስ አገራት ሻምፒዮና በነሐሴ የሚኖራቸው ተሳትፎንም ለማጣርያው ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረውም ገልፀዋል፡፡ የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ደግሞ በ1970 እና 80ዎቹ ለብሄራዊ ቡድናቸው የተጫወቱት ሞቺኒ ማቴቴ ናቸው፡፡ የሌሶቶ የምንግዜም ምርጥ ተጨዋች የሚባሉት ሞቺኒ ሃላፊነቱን ዘንድሮ የተረከቡት አስቀድመው የነበሩት አውሮፓዊ አሰልጣኝ ከሃላፊነት ከተነሱ በኋላ በምትክነት ነው፡፡
በ2016 ሩዋንዳ ለምታዘጋጀው አራተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ውድድር በሚደረግ የጥሎ ማለፍ ቅድመማጣርያ ለኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ተቀናቃኝ ሆኖ የሚቀርበውን የኬንያ ብሄራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ደግሞ የ53 ዓመቱ ስኮትላንዳዊ ቦቢ ዊልያምሰን   ናቸው፡፡ በተጨዋችነት ዘመን በተለያዩ የስኮትላንድ ክለቦች የተጫወቱት እና አሰልጣኝ ከሆኑ በኋላ ኪልሞርክ ከተባለ የስኮትላንድ ክለብ ጋር የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ያገኙት ቦቢ ዊልያምሰን፤ በአሰልጣኝነት ልምዳቸው የእንግሊዙን ክለብ ቼስተር ሲቲ፤ የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን፤ የኬንያውን ክለብ ጎሮማሃያ በማሰልጠን ሰርተዋል፡፡ በ2013 እኤአ ላይ የኡጋንዳን ብሄራዊ ቡድንን በመያዝ በቻን ውድድር የተሳተፉት ቦቢ ኬንያ ባሏት ምርጥ ተጨዋቾች ከኢትዮጵያ ተሽላ ቅድመ ማጣርያውን በማለፍ ለቻን ውድድር ትበቃለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ በኔፓል በተከሰተውና በሬክተር ስኬል 7.8 በተመዘገበው አሰቃቂ የርዕደ-መሬት አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ5ሺህ በላይ መድረሱ መረጋገጡን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
በርዕደ-መሬቱ የተጎዱ ዜጎችን የማፈላለጉና እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን የመድረሱ እንቅስቃሴ በአስቸጋሪ የአየር ንብረት ሳቢያ አዳጋች ሆኖ የቀጠለ ሲሆን እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ5ሺህ በላይ መድረሱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ ከ10ሺህ በላይ ሰዎችም የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፣ ፍለጋው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የሟቾችም ሆነ የቁስለኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ተገምቷል፡፡  
ኔፓልን መልሶ ለማቋቋም ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል ተብሎ እንደሚገመት ያስታወቀው ዘገባው፣ የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት በበኩሉ፤ በአደጋው የደረሰው ጥፋት እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት መግለጹን አስታውቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ላንግታንግ በተባለችው የኔፓል አካባቢ በደረሱ ሁለት የመሬት መንሸራተት አደጋዎች፣ ከ200 በላይ ሰዎች የደረሱበት እንደጠፋም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱሺል ኮይራላ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ዜጎችን ለመዘከር ባለፈው ማክሰኞ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ ሃዘን ያወጁ ሲሆን ባለፉት አስር አመታት በርዕደ-መሬት ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ዜጎች ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ እንደሚደርስም አስታውቀዋል፡፡
በአደጋው የተጎዱ ዜጎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የድረሱልኝ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሂሊኮፕተር የታገዘ እንቅስቃሴ እየተደረገ ቢገኝም፣ ከፍተኛ ዝናብና ውሽንፍር ከመኖሩና ከቦታዎቹ ተራራማነት ጋር በተያያዘ፣ በከፋ ሁኔታ በተጎዱ አካባቢዎች ፈጥኖ ለመድረስ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የቅዳሜው የኔፓል ርዕደ-መሬት ስምንት ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ተጠቂ እንዳደረገ ያስታወቀ ሲሆን፣ ለአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ እርዳታ የሚውል 15 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የተመድ ቃል አቀባይ ፋራህ ሃቅ እንዳሉት፤ የገንዘብ ድጋፉ ተጎጂዎችን ለመታደግ በመስራት ላይ የሚገኙ የሰብዓዊ ተቋማትን እንቅስቃሴ ለማሳደግና ለተጎጂዎቹ የመጠለያ፣ የውሃ፣ የመድሃኒትና የሌሎች አገልግሎቶች አቅርቦቶችን ለማሟላት የሚውል ነው።
ህንድ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ማሌዢያ፣ ፓኪስታን እና እስራኤል ተጎጂዎችን ለመርዳት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ አውሮፕላኖችን ወደ ኔፓል የላኩ ሲሆን አሜሪካ በበኩሏ ለፈጥኖ ደራሽ እርዳታ የሚውል 10 ሚሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ከመግባቷ በተጨማሪ የእርዳታ ድርጅቶቿን በአደጋው የተጎዱትን ዜጎች እንዲረዱ ወደ ኔፓል ልካለች፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

- ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው አልተሳተፉም
- ምዕራባውያን አገራት ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ አይደለም ብለዋል

 ዋና ዋናዎቹ የሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነጻና ፍትሃዊ አይሆንም በሚል ራሳቸውን ባገለሉበት የአገሪቱ ምርጫ የተወዳደሩት ፕሬዚዳንት ኡመር ሃሰን አልበሽር፤ 94.5 በመቶ ድምጽ በማግኘት በቀጣይም አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ መመረጣቸውን ቢቢሲ ዘገበ።የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ ሙክታር አል አሳም ባለፈው ሰኞ ከካርቱም በሰጡት መግለጫ፣ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት አልበሽር፤ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ያስታወቁ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በበኩሉ፤ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት 13.3 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ድምጽ የሰጡት አንድ ሶስተኛ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ አልበሽር በዘንድሮው የሱዳን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይህ ነው የሚባል ፉክክር እንዳልገጠማቸው የዘገበው ዘጋርዲያን በበኩሉ፣ ከተፎካካሪዎች መካከል የተሻለ ድምጽ ያገኙት ፌደራል ትሩዝ ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት ፋደል አልሳይድ ሹያብ መሆናቸውንና ያገኙት ድምጽም 1.43 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውቋል።ከሚያዝያ 5 ቀን ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በመላ አገሪቱ በተቋቋሙ 11 ሺህ የድምጽ ጣቢያዎች በተከናወነው የድምጽ አሰጣጥ ስነስርአት ላይ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ድምጽ አለመስጠታቸውንና ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው በተፎካካሪነት የቀረቡት 15 እምብዛም እውቅና የሌላቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎች ብቻ እንደነበሩም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ኖርዌይን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገራት፣ ላለፉት 25 አመታት ሱዳንን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አልበሽር፤ በከፍተኛ ድምጽ ያሸነፉበትንና ባለፈው ሰኞ የተከናወነውን የአገሪቱ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ነጻና ፍትሃዊ አይደለም፣ እውቅና አንሰጠውም ሲሉ የተቹት ሲሆን፣ የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂፒንግ በበኩላቸው፤ ለአልበሽር የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ልከዋል፡፡
ስቲስ ኤንድ ኢኳሊቲ ሙቭመንት የተባለው የአገሪቱ አማጺ ቡድን ባለፈው እሁድ በደቡብ ዳርፉር አካባቢ በሱዳን መንግስት ጦር ላይ በከፈተው ወታደራዊ ጥቃት የጦር ካምፕ ማውደሙንና የጦር መሳሪያዎችን መማረኩን ያስታወቀ ሲሆን፣ የአገሪቱ የጦር ሃይል በበኩሉ አማጽያኑ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ባደረገው ድብደባ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን አስታውቋል፡፡ በአየር ድብደባው 16 ሲቪል ዜጎች መሞታቸውንና ከ11 በላይ የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን የዘገበው አይቢታይምስ ነው፡፡
በዳርፉር ግጭት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ የቀረበባቸውና የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው የ71 አመቱ አልበሽር፣ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ሲሉ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡
ፕሬዚዳንት አልበሽር እ.ኤ.አ በ1989 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ አገሪቱን እየመሩ ሲሆን ሱዳንን ለረጅም ጊዜ በመምራት ቀዳሚው ሰው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ