ባለፈው ቅዳሜ በኔፓል በተከሰተውና በሬክተር ስኬል 7.8 በተመዘገበው አሰቃቂ የርዕደ-መሬት አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ5ሺህ በላይ መድረሱ መረጋገጡን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
በርዕደ-መሬቱ የተጎዱ ዜጎችን የማፈላለጉና እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን የመድረሱ እንቅስቃሴ በአስቸጋሪ የአየር ንብረት ሳቢያ አዳጋች ሆኖ የቀጠለ ሲሆን እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ5ሺህ በላይ መድረሱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ ከ10ሺህ በላይ ሰዎችም የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፣ ፍለጋው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የሟቾችም ሆነ የቁስለኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ተገምቷል፡፡  
ኔፓልን መልሶ ለማቋቋም ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል ተብሎ እንደሚገመት ያስታወቀው ዘገባው፣ የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት በበኩሉ፤ በአደጋው የደረሰው ጥፋት እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት መግለጹን አስታውቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ላንግታንግ በተባለችው የኔፓል አካባቢ በደረሱ ሁለት የመሬት መንሸራተት አደጋዎች፣ ከ200 በላይ ሰዎች የደረሱበት እንደጠፋም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱሺል ኮይራላ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ዜጎችን ለመዘከር ባለፈው ማክሰኞ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ ሃዘን ያወጁ ሲሆን ባለፉት አስር አመታት በርዕደ-መሬት ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ዜጎች ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ እንደሚደርስም አስታውቀዋል፡፡
በአደጋው የተጎዱ ዜጎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የድረሱልኝ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሂሊኮፕተር የታገዘ እንቅስቃሴ እየተደረገ ቢገኝም፣ ከፍተኛ ዝናብና ውሽንፍር ከመኖሩና ከቦታዎቹ ተራራማነት ጋር በተያያዘ፣ በከፋ ሁኔታ በተጎዱ አካባቢዎች ፈጥኖ ለመድረስ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የቅዳሜው የኔፓል ርዕደ-መሬት ስምንት ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ተጠቂ እንዳደረገ ያስታወቀ ሲሆን፣ ለአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ እርዳታ የሚውል 15 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የተመድ ቃል አቀባይ ፋራህ ሃቅ እንዳሉት፤ የገንዘብ ድጋፉ ተጎጂዎችን ለመታደግ በመስራት ላይ የሚገኙ የሰብዓዊ ተቋማትን እንቅስቃሴ ለማሳደግና ለተጎጂዎቹ የመጠለያ፣ የውሃ፣ የመድሃኒትና የሌሎች አገልግሎቶች አቅርቦቶችን ለማሟላት የሚውል ነው።
ህንድ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ማሌዢያ፣ ፓኪስታን እና እስራኤል ተጎጂዎችን ለመርዳት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ አውሮፕላኖችን ወደ ኔፓል የላኩ ሲሆን አሜሪካ በበኩሏ ለፈጥኖ ደራሽ እርዳታ የሚውል 10 ሚሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ከመግባቷ በተጨማሪ የእርዳታ ድርጅቶቿን በአደጋው የተጎዱትን ዜጎች እንዲረዱ ወደ ኔፓል ልካለች፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 በሰከንድ 10 ማይል፤ በሰዓት 603 ኪ.ሜ ይፈተለካል

በአለማችን በፍጥነቱ አቻ የማይገኝለት የተባለውና በጃፓን የተሰራው ፈጣን ባቡር ባለፈው ማክሰኞ ከብረወሰን ባስመዘገበ ፍጥነት የሙከራ ጉዞ ማድረጉን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡በጃፓኗ ያማናሺ ከተማ የሙከራ ጉዞ ያደረገው ባቡሩ፤ በሰዓት 603 ኪሊ ሜትር ፍጥነት ሲጓዝ ያዩት የአካባቢዋ ነዋሪዎች ያዩትን ነገር ለማመን ተቸግረው እንደነበር ዘገባው ገልጧል፡፡
እ.ኤ.አ በ2027 መደበኛ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ይሄው ፈጣን ባቡር፣ ከተለመደው አካሄድ በተለየ ሃዲዱን ሳይነካ በማግኔቲክ ፊልድ በ10 ሲንቲ ሜትር ከፍታ የሚጓዝ ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ በፊት የአለማችንን የፈጣን ባቡር ክብረወሰን ይዞ የነበረው፣ ሌላ የኩባንያው ምርት የሆነ ባቡር እንደነበረ ያስታወሰው ዘገባው፣ ይሄው ባቡር ከ12 አመታት በፊት በሰዓት 581 ኪሎሜትር ፍጥነት ተጉዞ እንደነበር ገልጧል፡፡
በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የአለማችን ፈጣን ባቡር በቻይና የተሰራና በሰዓት 431 ኪሎሜትሮችን የመጓዝ አቅም ያለው ነው፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

    ደብረብርሃን ዕድሜ ጠገብ ከተማ ናት። የሰሜን ከተሞች መተላለፊያ ናት፡፡ ከዕድገት ተለያይታለብዙ ዘመናት ብትቆይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያንቀላፋችበትን ጊዜ ለማካካስ፣  እየታተረች ነው፡፡
ከተማዋ ከባህር ጠለል በላይ በ2,700 ሜትር ከፍታ ላይ ስለምትገኝ ለኢንቨስትመንት አመቺ ናት። የከተማዋ አስተዳደር ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የኢንዱስትሪ ከተማ ሊያደርጋት እየተንቀሳቀሰ ነው። ለኢንቨስትመንት ማነቆ ሆነው የቆዩ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሰራሮችን በማሻሻል ላይ ይገኛል፡፡ ለኢንዱስትሪ በተከለሉ አራት መንደሮች መሰረተ ልማት የተሟላለት 256 ሄክታር መሬት አዘጋጅቷል። ለማኑፋክቸሪንግ መሬት በምደባ 1 ካ.ሜ በ0.50 ሳንቲም ይሰጣል፡፡ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልግ ግለሰብ ወይም ድርጅት ማስረጃዎች አሟልቶ ካቀረበ የጠየቀውን መሬት በአንድ ቀን ቢበዛ ደግሞ በሁለትና ሶስት ቀን እንደሚረከብ ተገልፆልናል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 18 የአገር ውስጥና የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ደብረ ብርሃን ከትመዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ በተለያየ ደረጃ ያሉ ናቸው፡፡ ምርት የጀመሩ፣ በግንባታ ላይ ያሉና መሬት ተረክበው መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠላቸው ይገኙበታል፡፡ ባለፈው ሳምንት አርብ ለ15 ኢንዱስትሪዎች የመሰረት ድንጋይ ለማኖር ቢታቀድም በጊዜ እጥረት የተነሳ የስድስቱ ብቻ ነው የተከናወነው፡፡ የሶስት ኢንዱስትሪዎች የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ በስፍራው ተገኝተን ነበር፡፡
በዕለቱ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠላቸው ሶስት ኢንዱስትሪዎች መካከል:- 1.2 ቢሊዮን ዶላር ከፍተኛ ካፒታል ያስመዘገበው የቱርኩ ጫማና የቆዳ ውጤቶች አምራች MY Shoes and Leather Manufacturing Plc ይገኙበታል፡፡ ማይ ሹዝ ፋብሪካ በቱርክ-አንካራ ትልቁ ጫማ አምራች ሲሆን በቀን 30ሺህ ጥንድ ጫማዎች እንደሚያመርት የኩባንያው ባለቤት ሚ/ር አህመት ኢሳን ባሰር ገልጸዋል፡፡
ምርታቸውን ለተለያዩ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና እስያ አገሮች እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ሚ/ር አህመት፣ ደንበኞቻችን በዝተው የምርት እጥረት አጋጥሞናል፤ የደንበኞቻችን ጥያቄ እየበዛ ነው። ስለዚህ ከ2010 ጀምሮ በአፍሪካ የት ኢንቨስት እንደምናደርግ ጥናት ስናደርግ ቆይተን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች የተረጋጋች፣ ለኢንቨስትመንት የሚጠየቀው ወጪ ዝቅተኛ፤ ለቢዝነስ አመቺ ሆና ስላገኘናት መረጥናት፡፡ እዚህ ስንመጣ ደግሞ የመንግሥት ድጋፍ ከጠበቅነው በላይ ሆኖ አገኘነው በማለት አስረድተዋል፡፡
የቱርክ ቀረጥ ከፍተኛ ስለሆነ በአገራቸው ካመረቱት ምርት የፈለጉትን ያህል ለአውሮፓ ህብረት አገሮች ማቅረብ እንዳልቻሉ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ የምትጠይቀው ቀረጥ ከቱርክ በጣም ያነሰ፣ ለሰራተኛ የሚከፈለው ዋጋ በጣም ተስማሚ፣ የኤሌክትሪክ ዋጋ ርካሽ፣ ከቱርክ ጋር ሲነፃፀር የምርት ወጪ እጅግ ዝቅተኛ ስለሆነ በማንኛውም የዓለም ገበያ መወዳደር ያስችለናል፡፡ በዓለም የሸቀጦች ዋጋ እየቀነሰ ስለሆነ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ትልቁ ጫማ አምራች እንሆናለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ለማይ ሹዝ ያስረከበው ቦታ 7 ሄክታር ሲሆን ፋብሪካው በ35ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ እንደሚያርፍ፣ የፋብሪካው ግንባታ ክረምቱ እንዳበቃ በመስከረም ወይም በጥቅምት ወር እንደሚጀመርና በአራት ወር ተጠናቆ በማርች 2016 ወደ ምርት እንደሚገባ ታውቋል፡፡
ግንባታውን በአራት ወር ለማጠናቀቅ የቸኮሉት ከፈረንሳይ፣ ከአሜሪካው ዎል ማርትና ከስፔይን ድርጅቶች ኮንትራት ስለተዋዋሉ ነው፡፡ የስፔይን ውላቸው ማርች 1,2016 ስለሆነ የፋብሪካው ግንባታ ባይጠናቀቅ እንኳ በከፊል ባለቀው ምርት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያው ምርት 30 ሺህ ሲንተቲክ (የተለያዩ ነገሮች ውህዶች) ከንፁህ ቆዳ 2ሺህ ጥንድ ጫማዎች የሚመረቱ ሲሆን እነዚህን ጫማዎች ወደ ውጭ በመላክ 26 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደሚገኝ፣ ለ1ሺ 962 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርና ይህ አኀዝ በ3ኛው ዓመት 3ሺህ እንደሚደርስ አብራርተዋል፡፡
ማይ ሹዝ ኤንድ ሌዘር ማኑፋክቸሪንግ በአራት አገራት በቱርክ፣ ኢትዮጵያ፣ ቻይናና በብራዚል ፋብሪካዎች ሲኖሩት፤ ትልቁ በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የሚገኘው ነው፡፡ ሁለተኛው ትልቅ ፋብሪካ በኢትዮጵያ የሚገነባ ሲሆን የቻይናው ፋብሪካ እዚህ የሚሰራውን ግማሽ ያህላል፡፡ በብራዚል ያለው በኢትዮጵያ ከሚሰራው በሩብ ያንሳል፡፡ “አሁን በአራት አህጉራት በአውሮፓ፣ በኤስያ፣ በደቡብ አሜሪካና በአፍሪካ ፋብሪካዎች አሉን” ብለዋል ሚ/ር አህመት ኢሳን ባሰር፡፡
ሌላው በዕለቱ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለትና የጥቁር አሜሪካዊው ኢንቨስተር የሚ/ር ብሪክስ ዋሽንግተን ንብረት የሆነው ጀኒፐር የብርጭ ጠርሙስ ፋብሪካ ነው፡፡
ጀኒፐር ጠርሙስ ፋብሪካ በ900 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ፋብሪካ ሲሆን በዓመት 150 ሚሊዮን ጠርሙሶች እንደሚያመርትና በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ሲጀምር በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ፋብሪካ እንደሚሆን የጀኒፐር ዋና ስራ አስፈፃሚና ጀነራል ማናጀር ሚ/ር ብሪክስ ዋሽንግተን ገልጸዋል፡፡
የፋብሪካው ግንባታ በ2015 አጋማሽ ተጀምሮ በ2016 አጋማሽ የሚጠናቀቅ ሲሆን ግንባታው 900 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ተብሏል::
 የፋብሪካው ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ አገር ገበያ ሲውል በየዓመቱ 30 ሚሊዮን ያህል ጠርሙሶች ለአፍሪካና ለሌሎች አገሮች ይሸጣሉ፡፡ ፋብሪካው ለ500 ያህል ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ታውቋል፡፡
በሁለቱ ፋብሪካዎች መካከል ለመሥራት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ራምስታድ የተባለ የሆላንድ ስሪት ትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ ነው፡፡
 አቶ ጥበበ ሰለሞን የቲሲቲ ኢንተርፕራይዝ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ “በአገር ውስጥ ከግብርና ሚ/ር እና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ አካላት ጋር በመሆን ከ200 በላይ ገበሬዎችን በማሳተፍ ሞክረንና ተማምነንበት ወደ ምርት ልንገባ ነው” ብለዋል፡፡
 ትራክተሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት የጠቀሱት አቶ ጥበበ፤ በ90 ሳ.ሜ 90 ኪ.ግ ክብደት ያለው 9 መከስከሻና ማረሻ እንዳለው፣ መሬቱ ለም ከሆነ በ8 ሰዓት ውስጥ 20 ሊትር በማይሞላ ነዳጅ 2 ሄክታር መሬት ለዘር እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል፡፡
መሬት ማረስ፣ የዘር ረድፍ ማበጀት፣ መዝራት (መትከል)፣ ቦይ ማውጣት፣ እህል መሰብሰብ፣ ማጓጓዝ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ ውሃ በቱቦ መሳብ … በእጅ እየተገፋ የሚያርሰው ትራክተር ከሚሰጣቸው ጥቅሞች ጥቂቱ ናቸው፡
በስፍራው በመገኘት የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለብርሃንና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ አህመድ አብተው ናቸው፡፡  

መመዘኛዎቹ ምን ምን ያካትታሉ?
“አንዳንድ ሆቴሎች ከምዘናው እያፈገፈጉ ነው”

     ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች እንደ ፍላጐታቸው አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል የተባለው የሆቴሎች ኮከብ ምዘና በአዲስ አበባ ከተጀመረ አንስቶ ወደ 40 የሚጠጉ ሆቴሎች ተመዝነው የኮከብ ደረጃ ወጥቶላቸዋል፡፡ የሁሉም ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ተዘጋጅቶ ከተጠናቀቀ በኋላ የትኛው ባለ 5፣ ባለ 4፣ ባለ 3 እና ባለ 2 ኮከብ እንደሆነ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በዋነኛነት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚያከናውነው የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምዘና፣ በአለማቀፍ የሆቴል ኤክስፐርቶች የሚከናወን ሲሆን ምዘናው በየ3 አመቱ ይከለሣል፡፡ ያኔ የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ እንደሚያስመዘግቡት ውጤት ከፍና ዝቅ ሊል እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡
እስካሁን ባለው ምዘና ሂደት ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን የጠቆመው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ አንዳንድ ሆቴሎች ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የተለያዩ ሰበቦችን እያስቀመጡ ከምዘናው ለመውጣት እየሞከሩ ነው ብሏል፡፡ “ግማሾቹ ገና እድሣት ላይ ነን” የሚል ምክንያት ያቀርባሉ ያሉት የምዘናው አስተባባሪ የስራ ሃላፊዎች፤ አንዳንዶቹም የሠራተኞቻቸውን ብቃት ለማስመዘን ዳተኝነት ታይቶባቸዋል ብለዋል፡፡ ለእንደነዚህ አይነቶቹ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሠራ ነውም ተብሏል፡፡ በቢሾፍቱ ከተማ በጉዳዩ ላይ በተደረገው የባለ ድርሻ አካላት ውይይት ላይ ሆቴሎች በተገቢው መንገድ ተፈትሸውና ተመዝነው የኮከብ ደረጃ ማግኘታቸው ለሀገር ገጽታ ካለው መልካም ፋይዳ አንፃር ምዘናው ግዴታ እንዲሆን የሚጠይቁ አስተያየቶችም ተሠንዝረዋል፡፡
ባለሙያዎችን በቢሾፍቱ ከተማ ያከራከረው የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምዘና፣ በተለይ በክልል የሚገኙትን ሆቴሎች ከመሠረተ ልማት ተደራሽነት አንፃር በአዲስ አበባ ከሚገኙት ነጥሎ እንዲመለከት ከአንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት የቀረበበት ቢሆንም ምዘናው አለማቀፍ እንደመሆኑ፣ በግልፅ የተቀመጡ የምዘና ዝርዝር መስፈርቶችም በመዘጋጀታቸው ያለምንም የተለየ ድጋፍና ልዩነት በክልል ያሉ ሆቴሎች ከአዲስ አበባ ካሉት እኩል ይመዘናሉ ሲሉ የምዘና ሂደቱ አስተባባሪዎች ምላሽ ሠጥተዋል፡፡
እስከ ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ ወደ 500 የሚጠጉ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሆቴሎች እንደሚመዘኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱል ቃድር የጠቆሙ ሲሆን ሆቴሎቹ በተለያዩ አካላት እንደሚመዘኑም ገልፀዋል፡፡
የእሣትና ድንገተኛ አደጋን የመከላከል አቅምን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉትን ሆቴሎች የአዲስ አበባ እሣትና ድንገተኛ መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የሚመዝን ሲሆን በተለይ በኦሮሚያ ክልል እና በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ሆቴሎችን ለመመዘን የሚያስችል የእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ ባለስልጣን አለመኖሩ አነጋጋሪ ነበር፡፡ ክልሎች የራሣቸው የእሣትና ድንገተኛ መከላከያ አደረጃጀት እንደሌላቸውም በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አሠፋ ከሲቶ፤ ሃገሪቱ በፌደራል ደረጃ የተዋቀረ የእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ ተቋም እንደሌላት ጠቅሰው ተቋሙን ለማቋቋም የተለያዩ ሠነዶች እየተዘጋጁና ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም የፌደራል እሣትና አደጋ መከላከያ ሲኖር ክልሎችም በየደረጃው የተጠናከረ መሰል ተቋም ይኖራቸዋል ተብሎ እንደሚታሰብ ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ለጊዜው ግን በክልሎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሆቴሎችን ከእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች አንፃር የሚመዝን አካል ማን ይሁን የሚለው ተጨማሪ ውይይት ያስፈልገዋል ተብሏል፡፡
ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምዘና ውስጥ ለመግባት የእሣትና ድንገተኛ መከላከያ አቅማቸው አስተማማኝነት ተረጋግጦ ሠርተፊኬት የሚሠጣቸው ሲሆን ከጤናና የስነምግብ መድሃኒት አስተዳደር ቢሮዎች አጠቃላይ የጤና እና የንፅህና አጠባበቅ ሠርተፍኬት ባለቤት መሆን ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
በዋናነነት ከ1-5 የኮከብ ደረጃ ባለቤት የሚያደርጋቸው ደግሞ የአለማቀፉ የቴክኒክ ኮሚቴ ለአጠቃላይ አገልግሎታቸውና የህንፃ ውስጣዊና ውጫዊ ገጽታ እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎት አይነቶች በወጣው የፍተሻ ዝርዝር ነጥቦች ላይ አመርቂ ውጤት ሲያስመዘግቡ ብቻ ይሆናል፡፡
ዝርዝር መመዘኛው ያካተታቸው ዋና ዋና ጉዳዮች
የኮከብ ደረጃ ለማግኘት የሚመዘን ሆቴል ቢያንስ 10 የአልጋ ክፍሎች ያሉት መሆን ይጠበቅበታል፤ ባርና ሬስቶራንት ከቁርስ፣ ምሣ እና እራት አቅርቦት ጋር ሊኖረው ይገባል፤ ከአደጋ ደህንነት፣ ከጤና እና ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ ከተቆጣጣሪ አካላት ሠርተፊኬት ማግኘት ይጠበቅበታል፤ የእንግዳ መቀበያ ክፍል (ሪሴፕሽን) ሊኖረው ይገባል፤ እንዲሁም  እያንዳንዱ ክፍል የራሱ መታጠቢያ እና መፀዳጃ ቤት እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት መሟላታቸው ተረጋግጦ በኋላ ወደ ዋናው ምዘና ከተገባ በኋላ የህንፃው የውጭኛው ክፍል የግንባታ ጥራትና ለግንባታ ግብአት የዋሉ ቁሶች የጥራትና የውበት ደረጃ ይገመገማል፡፡
 የግድግዳ ቀለም ውበት፣ ግድግዳው ከስንጥቅ ነፃ ስለመሆኑን የንፅህና ደረጃው እንዲሁም የመስታወት ጥራትና አጠቃቀሙ ነጥቦች ይሰጣቸዋል፡፡
ከውጫዊ የግድግዳና የህንፃ ውበት ጋር ተያይዞ የግቢው የአረንጓዴ ቦታ ይዞታ እና የመናፈሻ ቦታም ይዘትና ጥራት ይገመገማል፤ የመኪና ማቆሚያ ቦታ፣ የውጪና የውስጥ የደህንነት ጥበቃ ሁኔታም በዝርዝር ይታያል፡፡
ወደ መኝታ ክፍሎች ሲገባ ደግሞ የቤቱ የውስጥ ቅብ፣ ዲኮር፣ የፈርኒቸር ውጤቶች ጥራትና አይነት፣ ቴሌቪዥን፣ ስልክ፣ የፀጉር ማድረቂያ፣ የኤሌክትሪክ ሶኬት ደረጃ እና የቮልቴጅ አቅም ይገመገማል፡፡ በተለይ ባለኮከብ ለመሆን ያሰቡ ሆቴሎች በእያንዳንዱ የመኝታ ክፍል ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥንና የwi-fi ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሁም የአነስተኛ ባር አገልግሎት በመኝታ ክፍሉ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የውስጥ መስኮት መጋረጃዎች ጥራትና የውበት ደረጃም ይመዘናል፤ የጣራው ርቀት 2.86 ሜትር መሆን እንዳለበት የወጣው መስፈርት ጠቅሷል፡፡
 የአልጋ ስፋትን በተመለከተ ከ1 እስከ 3 ኮከብ የሚሰጣቸው ሆቴሎች የአልጋ ስፋታቸው ከ0.90 ሜትር በ1.90 ሜትር እስከ 1.35 ሜትር በ1.90 ሜትር አልጋ መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ባለ 4 እና 5 ኮከብ ሆቴሎች ደግሞ 1.40 ሜትር በ2 ሜትር የሆኑ አልጋዎችን መዘርጋት ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም እንደሆቴሎቹ አቅም የኪንግ እና ኪዊን መጠነ አልጋዎችን ጥራት ካላቸው ፍራሾች እና አንሶላዎች ጋር መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሆቴሎች ለሚረብሹ ድምፆች የመጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ መሆን እንዳለበት ያስቀመጠው መስፈርቱ፤ በአካባቢ የሚኖር ድምፅ ከ40 ዲሴብል በታች መሆን እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ ሆቴሎቹም ለድምፅ ብክለት ያላቸው ተጋላጭነት በዚህ ተገምግሞ ውጤት ይሰጣቸዋል፡፡
በእያንዳንዱ መኝታ ክፍል የመልበሻ መስታወቶች፣ የንባብ መፅሃፍትና ጋዜጣን ጨምሮ የተለያዩ ለእንግዳው ጠቃሚ የሆኑ ቁሳቁሶች መኖራቸውም የበለጠ ኮከብ ያስገኛል፡፡
 ከ3 እስከ 5 እና ከዚያ በላይ ኮከብ ማግኘት የሚፈልጉ ሆቴሎች የግዴታ የተለየ የሲጋራ ማጨሻ ክፍል ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለሁሉም ዓይነት ተጠቃሚዎች የሚውሉ አገልግሎቶችን በማቅረብ ረገድ ለኮከብ ደረጃ የሚወዳደሩ ሆቴሎች የውበት ሳሎኖች፣ የስጦታ እቃ መሸጫ ሱቆች፣ አበባ መሸጫ እንዲሁም ኬክ ቤቶች ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን የውጭ ገንዘብ ምንዛሬ አገልግሎት፣ የጉብኝት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች እና የታክሲ አገልግሎት ምን ያህል ፐርሰንት አሟልተዋል? የሚለው ተገምግሞ የኮከብ ማዕረጉ እንደነጥባቸው ይሰጣቸዋል፡፡
ከምግብ አቅርቦት ጋር በተገናኘም በዝርዝር የሚያቀርቡት የምግብ ዓይነትና ጥራት ተገምግሞ ነጥብ የሚሰጥ ሲሆን ባለ ኮከብ ሆቴሎች ሁሉም ቁርስ በነፃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የሻወር አገልግሎት በዓይነትና በጥራት፣ ሳውናና ጃኩዚ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን አገልግሎት በተለይ ለባለ 4 እና 5 ኮከብ ሆቴሎች የግዴታ ይሆናል፡፡
የመስፈርቱ መመዘኛ ነጥቦች ላይ በዝርዝር የቀረቡ የፍተሻ መጠይቆች የተካተቱ ሲሆን በዋናነት አንድ ሆቴል በሚያገኘው ውጤት መሰረት የኮከብ ደረጃ ለማግኘት የውጪ የህንፃ አካሉና አጠቃላይ የግቢ ገፅታው፣ የአልጋ ክፍሎቹ ጥራት፣ የመታጠቢያና ሽንት ቤት ጥራት፣ የህዝባዊ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች የአገልግሎት አይነት በጥራት መሟላት እንዲሁም የባር እና ምግብ አገልግሎቱ፣ የቤት ንፅህና አያያዝና ጥገና፣ የደህንነት አስተማማኝነቱና ብቁ ሰራተኞችና የስራ ኃላፊዎች መኖራቸው ይገመገማል፡፡
በአጠቃላይ ከተቀመጡት ነጥቦች ከ90 በመቶ በላይ ያገኘ ሆቴል ባለ 5 ኮከብ ሌግዠሪ ደረጃ ይሠጠዋል፡፡ ከ80 በመቶ በላይ ያገኘ 5 ኮከብ፣ ከ70 በመቶ በላይ 4 ኮከብ፣ ከ60 በመቶ በላይ 3 ኮከብ፣ ከ50 በመቶ በላይ 2 ኮከብ እንዲሁም ከ30 በመቶ በላይ ውጤት ያመጣ ባለ 1 ኮከብ ደረጃ ይሰጠዋል፡፡
የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ ውጤት (ማን ምን ደረጃ አገኘ የሚለው) በሰኔ መጨረሻ ይፋ እንደሚደረግ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የገለፀ ሲሆን አንዳንድ ሆቴሎች ምዘናውን የተለያዩ ምክንያቶች በመደርደር እያፈገፈጉ ከመሆናቸው በስተቀር ስራው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡   

 በቅርቡ የኢንተርኔትና የሞባይል ባንኪንግ ግብይት እጀምራለሁ አለ
ባለፈው ዓመት 26 ቢሊዮን ብር አገበያየ
      
   የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ትልቁ ሥራው ለአርሶ አደሩ መረጃ ማቅረብ መሆኑን ጠቅሶ አርሶ አደሩ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም ፈጣን፣ ትክክለኛና አስተማማኝ የግብይት መረጃ እንዲያገኝ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ምርት ገበያው፣ በአርሶ አደሩና በድርጅቱ ባሉ የአሠራር ችግሮች ዙሪያ ለመወያየት ባለፈው ማክሰኞ በአዳማ ከተማ ባካሄደው 3ኛው ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ የምክክር መድረክ፣ አርሶ አደሩ፣ ከኋላ ቀሩና ከባህላዊው የግብይት አሠራር ተላቆ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆን እየሠራ መሆኑን የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ገልፀዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ ከ2005 ጀመሮ በየዓመቱ ከኅብረት ሥራ ማኅበራትና ከዩኒየኖች ጋር የሚያደርጉት ምክክር ዓላማ፣ ዩኒየኖቹ፣ እንደችግር በሚያነሷቸው ለምሳሌ የምርት ደረጃ አሰጣጥ፣ የናሙና አወሳሰድ፣… የመሳሰሉ የአሠራር ችግሮች ላይ በመነጋገርና ግልጽ በማድረግ የምርት ግብይቱን ተሳታፊ አርሶ አደሮች ቁጥር ማብዛት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የምርት ግብይቱ የሚካሄደው በአዲስ አበባ ባለው ማዕከል መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ወደፊት፣ ግብይቱን በክልል ከተሞች ለማድረግ በሀዋሳ ከተማ የማዕከል ግንባታ መጀመሩን፣ በሌሎች የክልል ዋና ከተሞችም በነቀምቴ በጐንደር፣ በአዳማ ለማቋቋም መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሩ ፈጣንና ትክክለኛ መረጃ ኖሮት፣ በኢንተርኔት (ኦንላይን) የምርት ግብይት  እንዲጀምር እየሠራን ነው ያሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ለሦስት ዓመት ሲሠራ የቆየው የኢንተርኔት ግብይት፣ አዲስ አበባ ባለው ማዕከል ሙከራ ተደርጐ ጠንካራና ደካማ ጐኑ ከተለየ በኋላ፣ ድክመቱ ታርሞና ተስተካክሎ፣ የኢንተርኔት ግብይቱ በሌሎች የክልል ከተሞች ይጀመራል ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ባደረግናቸው ሁለት የምክክር መድረኮች የኅብረት ሥራ ዩኒየኖቹ የፋይናንስ፣ የአስተዳደር፣ ከምርት ገበያው ጋር ተቀራርቦ ያለ መሥራት ችግር እንዳለባቸው ተረድተናል ያሉት በምርት ገበየው የአባላትና አቅም ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ተሾመ፤ ከምርት ገበያው ጋራ ተቀራርቦ ለመሥራት በአዲስ አበባ ቢሮ ሊኖራቸው ይገባል የሚለው የማይቻል መሆኑን ተረድተን እዚያው ባሉበት፣ ለአስተዳደር ችግር ሥልጠናና የተለያዩ ድጋፎች መስጠታቸውን ገልፀዋል፡፡
አርሶ አደሩ አዲስ አበባ ባለው ምርት ገበያ ምን እየተከናወነ እንደሆን፣ የዓለም ገበያን ዋጋ በራሱ ቋንቋ በሞባይል ስልኩ አይቶ እንዲረዳ ሞባይል ባንኪንግ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት የሙከራ ሥራ መጀመሩን ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰው፤ የአፕሊኬሽን ሶፍትዌሩ፣ በምርት ገበያው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ክፍል መዘጋጀቱን፣ 200 ኮምፒዩተሮች ተገዝተውና ባለሙያዎች ሠልጥነው የሙከራ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
የሞባይል ባንኪንግ ሙከራ ቢጀመርም አርሶ አደሩ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆነው ከ5 ዓመት በኋላ እንደሆነ ገልጸው፣ እስከዚያው ድረስ አጠቃቀሙን ሊረዱ ይችላሉ የሚሏቸውንና በቅርብ ያሉ አርሶ አደሮችን ስለአጠቃቀሙ እያሠለጠኑና እያስተማሩ የውሸት ግብይት በማድረግ እንዲለማመዱ፣ ከዚያም ከእነዚህ ሰዎች ጋር በመሆን ሌሎቹን አርሶ አደሮች ስለአጠቃቀሙ እንደሚያስተምሩ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ የምክክር መድረክ ከተለያዩ ዩኒየኖች የተገኙ አመራሮች አለብን ያሏቸውን ችግሮች አቅርበው ከመድረክ መሪዎቹ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አቶ ዘለቀ ማሞ የመተማ ዩኒየን የግብይት ክፍል ኃላፊ ሲሆን በአካባቢው ያሉ የመጋዘን ሠራተኞች የሚፈጽሙበትን በደል ተናግሯል፡፡
እኛ ወደ መጋዘን ለምናስገባው ምርት ኦሪጅናል ደረሰኝ ሳይሆን ኮፒ ነው የሚሰጡን፡፡ ቀሻቢዎቹ (ናሙና ወሳጆቹ) እያንዳንዱን ኬሻ 3 ቦታ ቀደው ናሙና ይወስዳሉ፣ ኬሻ መቅደጃው ሰፊ ከመሆኑም በላይ የቀደዱትን ቦታ አይከድኑትም፡፡ በዚህ የተነሳ፣ ከአንድ መኪና ከ3-5 ኪ.ግ ይፈሳል፡፡ ለናሙና ምርመራ የሚወሰደው 8 ኪሎ ነው ቢባልም ከዚያ በላይ ነው የሚወሰደው፡፡ ምርመራውን ካደረጉ በኋላ ለእኛ 1 ኪሎ ሰጥተው ቀሪው የት እንደሚገባ አናውቅም፡፡ ከአንድ መኪና ለቅሸባ የሚወሰደው ትንሹ 3 ኪሎ፣ ትልቁ 8 ኪሎ ነው፡፡ ይኼ እኛን ይጐዳናል፡፡ ሥራቸው ወጥነት የለውም፡፡
ለምሳሌ 400 ኬሻ ጭኖ የገባ መኪና ምርቱ እዚያው ላይ እንዳለ ለመመርመር አያመችም፡፡ ስለዚህ 250 ኬሻ ወርዶ ይመራመራል፡፡ ሌላ ሰው ሲያቀርብ የሚወርደው ኬሻ 210 ነው፡፡ ከእኛ 40 ኬሻ ትርፍ እንዲወርድ ይደረጋል፡፡ ወዛደሮች ሲያወርዱ 5 ብር፣ መልሰው ሲጭኑ 5 ብር ያስከፍሉናል፡፡ ለ40 ኬሻ 400 ብር እንከፍላለን፡፡ 50 መኪና ጭኜ ብወስድ ምን ያህል እንደምከፍል አስቡት፡፡ ለምን ከ210 ኬሻ በላይ እንዲወርድ አደረጋችሁ? ብለን ኃላፊውን ስንጠይቅ በቂ መልስ አይሰጠንም፡፡
እኛ ምርታችንን ወደ መጋዘን የምንወስደው አበጥረን፣ አናፍሰንና በአዲስ ኬሻ አድርገን ነው፡፡ በዚህ ዓመት የጥራት ደረጃ ሲያወጡ የሚሰጡን UG እና ደረጃ 4 ነው፡፡ UG (Under grade) ከደረጃ በታች ማለት ነው፡፡ የጥራት ደረጃው ከፍተኛ ለሆነው የሚሰጠው ደረጃ 1 ሲሆን ደረጃ 4 መጨረሻ ማለት ነው፡፡ ደረጃ አሰጣጡ ግልጽና ትክክል ስላልሆነ እየከሰርን ነው…በማለት የመጋዘን ሠራተኞች የሚፈጽሙበትን በደል አስረድቷል፡፡
በክልሎች አሠራር እኛም የምናያቸው አንዳንድ ጉድለቶች አሉ፡፡ የሚሠራው በሰው እስከሆነ ድረስ ችግሮች አይኖሩም ማለት አይቻልም፡፡ ችግሮቹ በሁለቱም ወገን የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ ማለትም ምናልባት ሠራተኞቹን ጉርሻ አስለምደው ይሆናል፡፡ ሰጪ ከሌለ ተቀባይ አይኖርም፡፡ ሠራተኞቹ የለመዱትን ነገር ሲያጡ የተፈጠረ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ካለ የመጋዘን አስተዳደር ደንብ ስላለ በዚያ መሠረት አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል አቶ ኤርምያስ ተሾመ፡፡
ሥልጠና ወስደው ክልል የተመደቡ ሰዎች የጥራት ደረጃ አሰጣጣቸው ትክክል መሆኑን ከአዲስ አበባ ባለሙያዎች እየተላኩ ይከታተላሉ፡፡ ኦሪጂናል ደረሰኝ አይሰጡንም የተባለው ማስተካከል ስለሚቻል ቀላል ነው፡፡ ችግሩ መኖሩን የሰማነው ገና ዛሬ ነው፡፡ የተባሉት ችግሮች መኖራቸውን አጣርተን እውነት ከሆነ ጥብቅ አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን በማለት አቶ ኤርሚያስ  ገልፀዋል፡፡
ከሰባት ዓመት በፊት በ2000 ዓ.ም ሁለት ምርት በማገበያየት በ100 መሥራች አባላት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፤ በአሁኑ ወቅት 6 ዓይነት ምርቶች ይገበያያል፡፡ 14‚725 ደንበኞች ያላቸው 346 ሙሉ አባላት፣ 19 ቅርንጫፎችና 56 መጋዘኖች አሉት፡፡ አምና  586‚164 ሜትሪክ ቶንስ እህል አሻሽጦጠ ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ  ማስገኘቱ ታውቋል፡፡
የምክክር መድረኩን የኢትዮጵያ ምርት ገበያና የምርት ገበያ ባለሥልጣን ከፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው፡፡ 

የስኳር፣ የደም ግፊትና የልብ ህመም ችግርዎን በሞባይልዎ መቆጣጠር ይችላሉ
የሞባይል ስልክ ጨረሮች የወንዶችን የወሊድ ብቃት ይቀንሳሉ

     ኤሌክሳንድር ግርሃም ቤል ስልክን ፈልስፎ ለዓለም ሲያበረክት ቴክኖሎጂው የሰዎች ለሰዎች ግንኙነትን ብቻ ሳይሆን የየዕለት ተግባራቸውን ለማቅለልና ለማቀላጠፍ የሚረዳ አጋራቸው ይሆናል የሚል ግምት አልነበረውም፡፡ ሰዎችን እርስ በእርስ በድምፅ በማገናኘት የተጀመረው የስልክ ቴክኖሎጂ፤ በወቅቱ እንደ ተዓምር ነበር የታየው፡፡
ቴክኖሎጂው ቀስ በቀስም እየተሻሻለና እያደገ ሄደ፡፡ አሁን ቴክኖሎጂው ሰዎች የዕለት የጤና ሁኔታቸውን የሚከታተሉበት የቅርብ ዶክተራቸው እስከመሆን ደርሷል፡፡
ዓለም አቀፍ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ዩኒየን ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአለም አቀፍ ደረጃ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ 5 ቢሊዮን የሚጠጋ የዓለማችን ህዝብ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡
ተንቀሳቃሽ ስልኮች ከሚሰጧቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል የሰዎችን የዕለት ተዕለት ተግባራት ቀላል፣ ምቹና የተቀላጠፈ ማድረግ፣ መልዕክቶችን በቀላሉ ለመላክና ለመቀበል ማስቻል፣ መረጃዎችን በፍጥነት ማድረስ፣ እንደ ባንክና ኢንሹራንስ ካሉ ድርጅቶች ጋር የሚኖረንን የሥራ ግንኙነት ምቹና ቀልጣፋ ማድረግ ጥቂቶቹ ሲሆኑ እድሜ ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች! ዛሬ ለገበያ የሚቀርቡት የተንቀሳቃሽ ስልክ ቴክኖሎጂዎች የተጠቃሚውን የጤና ሁኔታ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሆነዋል፡፡
የስኳር፣ የደም ግፊትና የልብ ህመም ችግርን በተንቀሳቃሽ ስልክ ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚያስችል ቴክኖሎጂን በመስራት ስልክን ተንቀሳቃሽ የግል ሐኪም አድርገውታል፡፡ ይሁን እንጂ እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ይኸው ተንቀሳቃሽ ስልክ፤ በአጠቃቀም ችግርና በራሱ በቴክኖሎጂው ተፈጥሮአዊ ባህርይ ምክንያት የሚያስከትላቸው አደገኛ የጤና ችግሮችም አሉ፡
ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ለተጠቃሚው እጅግ አደገኛ ከሚያደርጓቸው ጉዳዮች መካከል ጨረሩ በቅድሚያ ይጠቀሳል፡፡ የሬዲዮ ሲግናልን ይዘው የሚረጩት ጨረሮቹ ለጤና እጅግ አደገኛ ችግሮችን ያስከትላሉ፡፡ በሞባይል ስልክ አጠቃቀም ወቅት ስልኩ ተግባሩን እንዲከውን የሚያደርጉት ጨረሮች በቅድሚያ የሞባይል ስልኩን አንቴና ያገኙታል፡፡ ይህ አንቴና ደግሞ የስልክ ተጠቃሚው በሚነጋገርበት ወቅት ከጆሮ ግንዱ ስር በመሆን መልዕክቱን እንዲቀበል የሚያደርገው ነው፡፡ ቦታው ከአንጎላችን ጋር ተቀራራቢ ከመሆኑ አንጻር ደግሞ በሞባይል ስልኩ አንቴና ለሚረጩት ጨረሮች በቀላሉ ተጠቂ ይሆናል፡፡ በዚህ ሳቢያም የአንጎላችን የነርቭ ሥርዓት በጨረር ሊጎዳና ለከፍተኛ ጉዳት ሊጋለጥ እንደሚችል Environmental Health Perspectives የተሰኘ የጥናትና ምርምር መፅሔት ዘግቧል፡፡ በሞባይል ስልክ የሚለቀቀው ጨረር ከሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች መካከል ካንሰር፣ ከፍተኛ የልብ ህመም ተጠቃሽ ሲሆኑ ጨረሩ በአንጎላችን ውስጥ የሚገኘውንና አንጎላችንን ከተለያዩ መርዛማ ኬሚካሎችና ያልተፈለጉ ንጥረ ነገሮች የሚጠብቀውን “ብለድ ብሬይን ባርየር” የተባለውን ክፍል ሊጎዳውና ከጥቅም ውጪ ሊያደርገው እንደሚችል የምርምር መፅሄቱ ጠቁሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሞባይል ስልክ የሚለቀቀው ጨረር የወንዶችን የወሊድ ብቃት እንደሚቀንሰውና ለስንፈተ ወሲብ ሊያጋልጥ እንደሚችል መረጃው አመልክቷል፡፡ የተጠቃሚው ለጨረሩ ተጋልጦ የመቆየት መጠንና የመጋለጥ ዓይነቱ የሚደርስበትን የጉዳት መጠንም እንደሚወስነው መረጃው ገልጿል፡፡
ሞባይል ስልኮች የጤና ጠንቅ በሆኑ ባክቴሪያዎች የተበከሉ ናቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ በአሜሪካ የተደረገ አንድ ጥናት እንደገለፀው፤ በሞባይል ስልክ ቀፎዎች ላይ የተገኙት ባክቴሪያዎች እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ በእጅ ንክኪ አሊያም በትንፋሽ ሊተላለፉ የሚችሉ አደገኛ የበሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች በስልክ ቀፎዎቹ ላይ ተገኝተዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሞባይል ቀፎ አምራች ኩባንያዎች ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በስልክ ቀፎ መሸፈኛዎች ላይ ፀረ ባክቴሪያ ሽፋኖችን በመለጠፍ ባክቴሪያዎቹ ወደቀፎው በሚተላለፉበት ወቅት የጤና ጠንቅነታቸውን ያስቀረዋል፡፡
ለሞባይል ስልክ አጠቃቀም የሚረዱ ነጥቦች
በሞባይል ስልኮች ጨረር በከፍተኛ መጠን መጋለጥ የጤና ሥጋት መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ ስለዚህም በተቻለ መጠን ለሞባይል ስልኮች ጨረር የምንጋለጥበትን ሁኔታ መቀነስ ይገባል፡፡ ለዚህም በተቻለ መጠን መልዕክቶችን በፅሁፍ መልዕክት (SMS) መቀባበል የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ይመከራል፡፡
የሞባይል ስልኮችን እንደ ጡት ባሉ አካባቢዎች ከመያዝ መቆጠብ፡፡ ወንዶች የተጣበቀ ሱሪ ለብሰው ሞባይል ስልኮቻቸውን በሱሪ ኪሳቸው ውስጥ ሲይዙ ጥሪ በሚያሰማበት ወቅት ከስልኩ የሚወጣው ጨረር በወንዶች የፆታዊ አካላት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ስለዚህም ስልኮችን በእጅ ቦርሳና ሰፋ ባሉ ልብሶች፡- ኮት፣ ጃኬትና መሰል አልባሳት መያዝ በስልክ ጨረር ሳቢያ የሚደርሰውን ጉዳት ሊያስቀር ይችላል፡፡
ሞባይል ስልኮቻችን የበርካታ ባክቴሪያዎች መራቢያና የበሽታ አምጪ ቫይረሶች መከማቻ ስለሚሆኑ እጃችንን በንፁህ ውሃና በሳሙና ሳንታጠብ ከመመገብ መቆጠብ፣ ስልኮቻችንን በየጊዜው በአልኮል እንዲሁም በፀረ ባክቴሪያና በማፅጃ ኬሚካሎች በማፅዳት በበሽታ ከመያዝ ራሳችንን ልንታደግ እንደምንችል ጥናቱ አመልክቷል፡፡  

Published in ዋናው ጤና
Saturday, 02 May 2015 11:50

የኩከምበር ፋይዳ!

  ኩከምበር (የፈረንጅ ዱባ) ጀምግባችን ውስጥ አዘውትሮ የማይካተትና አብዛኛዎቻችን የማንመገበው የአትክልት አይነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ተክል ሰውነታችን በዕለት ከሚያስፈልጉት የንጥረ ነገር ፍጆታዎች አብዛኛዎችን አካቶ የያዘና ለጤና እጅግ ጠቃሚ  ነው፡፡
ቫይታሚን ቢ1፣ ቢ2፣ ቢ3፣ ቢ5፣ እና ቢ6፣ ፎሊክ አሲድ፣ ቫይታሚን ሲ፣ ካልሲየም፣ አይረን፣ ማግኔዚየም፣ ፎስፌት ፖታሲየም እና ዚንክን ይዟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኩከምበር በቂ ስኳር እና ኤሌክትሮላይትስ የተባሉ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ነው፡፡ እነዚህ ለሰውነታችን እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮቹን ሁሉ አካቶ የያዘው ኩከምበር ምን ጠቀሜታዎች አሉት? ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡
ድካም ሲሰማዎት
ከድካም ስሜትዎ ለመላቀቅና እንቅልፍ እንቅልፍ እያሰኘ ከሚጫጫንዎ የድብርት ስሜት ለመንቃት ወፈር ያለ ቡና አዘው ይሆናል … እስቲ ቡናዎን ያስቀምጡና በቀጫጭኑ የተቆራረጡ ጥቂት የኩከምበር ቁራጮችን ይመገቡ፡፡ ድካምዎ ጠፍቶ ስሜትዎ ሲነቃቃ ይሰማዎታል፡፡ የቫይታሚን ቢዎችና የካርቦ ሃይድሬትስ መገኛ የሆነው የኩከምበር ፍሬ ለድካም ፍቱን መድኀኒት ነው፡፡
ሃንግኦቨር ወይንም ከባድ የራስ ምታት ይዞዎታል?
ከከባድ አልኮል መጠጥ በኋላ ወይንም የራስ ምታት ህመም ሲሰማዎ ጥቂት የኩከምበር ቁራጮችን ይመገቡና ለጥቂት ደቂቃዎች አረፍ ይበሉ፡፡ የስኳር፣ የቫይታሚን ቢ እና የኤሌክትሮላይትስ መገኛ የሆነው ኩከምበር ሃንግኦቨርዎን አጥፍቶ፣ ከከባድ የራስ ምታት ህመምዎ ይገላግልዎታል፡፡ ሰውነታችን የራስ ምታት ህመም የሚያጋጥመው ከላይ የተገለፁት ንጥረነገሮች ሲያንሱት ነው፡፡
አካልዎም ሆነ መንፈስዎ ድካም ሲሰማው
ወደ ማሳጅ ቤቶች ሄደው ሰውነትዎን ዘና የሚያደርጉ እሽታዎችን ለማግኘት ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ሆኖም በቀላሉ አንድ የኩከምበር ፍሬን ቆራርጠው በሙቅ ውሃ ውስጥ ይዘፍዝፉትና በእሳት ጥደው እንዲፍለቀለቅ ያድርጉት፡፡ እንፋሎቱ ደስ የሚል የመዝናናት ስሜት ከመፍጠሩም በላይ ለአፍንጫ ደስ የሚያሰኝ ጠረንም ያመነጫል፡፡ ይህ በተለይ ለአራስ እናቶች ጠቀሜታው የትየለሌ ነው፡፡
የአፍ ጠረን ችግር አለብዎ?
አንድ የኩከምበር ቁራጭ ወስደው በምላስዎ የላይኛው ክፍልና በላንቃዎ መካከል አጣብቀው ለ30 ሰከንዶች ያህል የያዙት፡፡ መጥፎው የአፍ ጠረንዎ በፍጥነት ይወገዳል፡፡ በኩከምበር ውስጥ የሚገኘው ፓይቶኬሚካል የሚባለው ንጥረነገር በአፍ ውስጥ የሚገኙና ለመጥፎ ጠረን መንስኤ የሚሆኑ ባክቴሪያዎችን ይገድላል፡፡
የሻወር ቤት መስታወትዎ ጉም እያዘለ ያስቸግርዎታል?
ሻወር ከወሰዱ በኋላ የሻወር ቤት መስታዎትዎ ጉም እያዘለ የሚያስቸግርዎ ከሆነ በኩከምበር ቁራጭ መስታወትዎን ያፅዱ፡፡ በሚገርም ሁኔታ መስታዎትዎ ጥርት ያለ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ የመታጠቢያ ቤትዎ የስፓ አይነት ጠረን እንዲኖረው ያደርግልዎታል፡፡
በተለያዩ ነገሮች ለተበላሹ ወረቀቶችና የቤትዎ ግድግዳ …
የቤትዎ ግድግዳ ላይ በተለያዩ ቀለማት የተፃፉ ፅሁፎችን ወይም በጭቃና በልዩ ልዩ ነገሮች የተበላሸ የቤትዎን ግድግዳ በኩከምበር ቁራጭ ቀስ እያሉ ይፈግፍጉት፡፡ ግድግዳዎ ወደ ቀድሞ መልኩ ይመለሳል፡፡ በእስክሪብቶ እየፃፉ ሲሳሳቱም፣ የተሳሳቱትን ጽሁፍ በኩከምበር ቁራጭ ቀስ እያሉ ያጥፉት፡፡

Published in ዋናው ጤና

       ቦኩ ከአዳማ ከተማ ምሥራቃዊ ክፍል አምስት  ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ስፍራ ነው። ጥቅጥቅ ያለ ደን ያለበት፣ የተፈጥሮ እንፋሎት የሚፈልቅበትና ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ጅብና ሌሎች የዱር እንስሳት የሚፈነጩበት ድንግል የተፈጥሮ አካባቢ ነው፡፡ ከቦኩ ገደላማ ቦታ ላይ ሆኖ ቁልቁል ሸለቆውን፣ ገጸ ምድሩን፣ ልዩ ልዩ የዛፍ ዓይነቱን ሲመለከቱት  መንፈስን ያድሳል፡፡ በአጭር ርቀት አረንጓዴ የሆነውን የወንጂን የሸንኮራ አገዳ ተክል በሠፊው ሜዳ ላይ ተዘርግቶ ሲያዩት ልብን በተስፋ ያለመልማል፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ ታላላቅ ሰዎች ሳይቀሩ በቦኩ የተፈጥሮ ደን ውስጥ በመገኘት የአደን ሥነ ሥርዓት ያካሂዱበት ነበር፡፡ ሰሞኑን የጤና እክል ገጥሞኝ ወደ ቦታው ሄጄ በነበረበት ሰዓት መምህሬ ጀንበሬ ብዙ ወርቅ የተባሉ የእንፋሎቱ ደንበኛና ቋሚ ተጠቃሚ እንዲሁም የመቂ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አዛውንት እንዳጫወቱኝ፤ የቀድሞው ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በደጃዝማችነታቸው ዘመን ከነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ጋር ወደ ሥፍራው በፈረስ እየሄዱ ድኩላና ሌሎች የዱር እንስሳትን ያድኑ ነበር፡፡
ደጃዝማቹ አደን በሚያድኑበት ሰዓት ከቦኩ ገደል ሥር እንደ ጭስ እየተነነ የሚወጣውን የተፈጥሮ እንፋሎት ይመለከታሉ፡፡ ይህ እንፋሎት የሕዝብ መታከሚያ እንዲሆን በማሰብ በነጋድራስ ተሰማ እንዲጠና ካደረጉ በኋላ እንዲመሠረት ያደርጋሉ፡፡
መምህሬ ጀንበሬ ያኔ የ27 ዓመት ወጣት ነበሩ። በተፈጥሮ እንፋሎቱ ለመጠቀም በ1947 ዓ.ም ወደ ቦኩ ሲሄዱ ለጸበልተኞች ማረፊያ ትንሽዬ ሣር ቤት በመሠራት ላይ ነበረች፡፡
የሳር ቤቷ ግድግዳ ቆሞ ሣር ከዳኝ ይጠፋል፡፡ እርሳቸውም ዕውቀቱ ስለአላቸው “እኔ ልክደነው” ብለው በቀን 1.50 ሳንቲም እየተከፈላቸው ቤትዋን  አሳምረው በሣር ክፍክፍ ይከድኑዋታል፡፡ በወቅቱም በአካባቢው የነበሩ ነዋሪዎች ጠላ፣ ቆሎ እንጀራ፣ ዳቦ፣ ለጸበልተኛው ያቀርቡ ነበር፡፡ ያኔ ዝንጀሮዎችና ጦጣዎች ራቅ ብለው ድርጊቱን ከመመልከት በስተቀር እንዲህ እንደዛሬው ዓይን ያወጡ ዋና ተዋናዮች አልነበሩም፡፡
በወቅቱ የተፈጥሮ እንፋሎቱ የቦኩ ሚካኤል ጸበል እየተባለ ከመጠራቱም ባሻገር ሰው በተለምዶ የእንፋሎት መታከሚያ ክፍሎችን ገብርኤል፣ አቦ፣ ማርያም እያለ ይጠራቸው ነበር፡፡
በኋላ ላይ የተፈጥሮ እንፋሎቱን ከእምነት በተላቀቀ መልኩ ለሁሉም የእምነት ተከታዮች መታከሚያ እንዲሆን ስለታሰበ የየትኛውም እምነት ተከታይ ይገለገልበታል፡፡ እንዲያውም የእንግዳ ማረፊያ ቤቶችም በቆርቆሮ እንዲሠሩ ተደርጐ አገልግሎት ሲሰጥ በነበረበት ሰዓት አንድ ባለሥልጣን ታክመው ስለዳኑበት መብራት እንዲገባለት እንዳደረጉ መምህሬ ጀምበሬ አውግተውኛል፡፡ የቦኩ ሚካኤልም ከአካባቢው ተነሥቶ ከዋናው አዳማ ከተማ መግቢያ በር ላይ በዘመናዊ ፕላን ቤተክርስቲያኑ በካቴድራል መልክ እንዲገነባ ተደርጓል፡፡ በዚህ ረገድ የተፈጥሮ ሀብቱን መንግሥትም፣ ግለሰብም ሲያስተዳድረው የቆየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ዲንሾ የተባለ ድርጅት ተረክቦ፣ ዘመናዊ የእንግዳ ማረፊያ ቤቶችን፣ የአልጋ ክፍሎችን ካፊቴሪያዎችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች አገልግሎት ከመስጠቱ ባሻገር እንግዶች እንዳይጉላሉ ከአዳማ ቦኩ አድርሶ የሚመልስና በየቀኑ የሚመላለስ ተሽከርካሪ መድቦ የሕዝቡን ችግር አቃልሏል፡፡ በተለይ ለ1ኛ ደረጃ የእንፋሎት ክፍሎች ተጠቃሚዎች የዘመናዊ ሻወር አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከርም አዘጋጅቷል፡፡ ዘመናዊ የእንፋሎት መገልገያ ክፍሎች ኃይለኛ የሙቀት መጠን በማመንጨታቸው ምክንያት ተጠቃሚዎች በተለምዶ “ጥቁር አንበሳ”፣ “ፌደራል ፖሊስ”፣ “መከላከያ”፣ “ጤና ጥበቃ”፣ ትምህርት ሚኒስትር” ብለው ይጠሯቸዋል፡፡ በደረጃ በተከፋፈሉት የተፈጥሮ እንፋሎት መገልገያ ቦታዎችም ሰው ደስ ብሎትና በጥሩ ሁኔታ ተስተናግዶ ወደመጣበት ይመላል፡፡
በተለይ የመታጠቢያ ውሃ በባልዲ የሚያቀርቡና ክፍሎቹን ሰው ተጠቅሞ በወጣ ቁጥር አጽድተው ለአገልግሎት የሚያዘጋጁ ወጣቶች ታታሪነት በእጅጉ ያስደንቃል፡፡ ነገር ግን በቦኩ የእንፋሎት መገልገያ ቦታ ጧት፣ ሌሊትና ማታ አካባቢውን መድፍ የተተኮሰ ያህል የሚያናውጠው የጅብ ጩኸት፣ ስልት ያለው የዝንጀሮዎችና የጦጣዎች ቅሚያና ዘረፋ አያድረስ ያሰኛል፡፡
መንገደኛ ገና ከመኪና ሲወርድ ዝንጀሮዎችና ጦጣዎች እጅብ ብለው ወደ ሰው ሲመጡ መልካም አቀባበል ለማድረግ ያሰቡ ይመስላሉ፡፡ መንገደኛው አገልግል፣ ፌስታል፣ ሻንጣ፣ ሊያንጠለጥል ይችላል። እነ አጅሬ ያዩትን ነገር ከመቅጽበት ላፍ አድርገው ይሮጣሉ፡፡ በየመኝታ ክፍሉም እየገቡ ይዘርፋሉ። ምግብ፣ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ሞባይል፣ ልብስ በፌስታል… የተያዘ ነገር ነጥቀው ይሮጣሉ፡፡ እነዚህ ማጅራት መቺዎች የካፍቴሪያና የአልጋ መስተዋቶችን ሰባብረው ጥለዋቸዋል፡፡ በተለይም ካፍቴሪያዎች ኮርኒስ ስለሌላቸው ጦጣዎች ተንጠልጥለው ይገቡና ከወራጁ ላይ ይሠፍራሉ፡፡ ምግብ በሚቀርብበት ሰዓት ከላይ ሆነው ሽንታቸውን በምግቡ ላይ ይለቁታል፡፡ ሊበላ ያሰፈሰፈ ሁሉ፤ “አይ አይ አይ” በማለት ምግቡን ወደ ውጭ ሲደፋው ተንደርድረው በመውረድ እየተሻሙና እየተጣሉ ይበላሉ፡፡
የዝንጀሮ መንጋው ሰላማዊ መስሎ እየተንጐማለለ በካፊቴሪያ ዙሪያ ይሠፍራል፡፡ ያላወቀ ሰው ምግብ አዝዞ ሊበላ ሲል መስተዋቱ በረገፈው ግድግዳ በኩል እጁን ልኮ ከመቅጽበት ምግቡን ይዞት ይሮጣል፡፡ አንዲት ሴትዮ ከመኪና እንደወረዱ እንጀራ በአገልግል ታቅፈው ጉብሲስ ጉብሲስ እያሉ ሲራመዱ፣ አንድ ትልቅ ጉመሬ ትልቁን አገልግል በቅጽበት ላፍ አደረገና ወደ ላይ ወደ ገደሉ ይዞት ወጣ፡፡
ወዲያው አገልግሉን ፈታታና ለሳምንት የተያዘውን ስንቅ ብቻውን ጠብ አደረገው፡፡ ከዚያ ቆየና አገልግሉን ወደታች ሲወረውረው አገልግሉ ተንከባልሎ በእልህና በንዴት ሲንጨረጨሩ ወደነበሩት አሮጊት ዘንድ ደረሰ፡፡ “ተመስጌን እንኳን አገልግሌን ሰጠኸኝ” ብለው ዝንጀሮውን አመሰገኑት። የዱር እንስሳቱን ብልጠት ሰው ሁሉ እንደ መዝናኛ ከመመልከት ውጭ የሚጨክንባቸው የለም፡፡
የዝንጀሮ እና የጦጣ መዛለያ የሆኑት የጣሪያ ቆርቆሮዎች ተጣመዋል፣ ረግበዋል፡፡ በቦኩ አካባቢ ያሉ ዝንጀሮዎችና ጦጣዎች ከሰው ጋር ማኅበራዊ ኑሮ ስለመሠረቱ የዕለት ምግባቸውን ለማግኘት ወደ ጫካ ከመሠማራት ይልቅ እየቀሙ መኖርን ተለማመደውታል፡፡ ሰው መፍራትም ማፈርም ትተዋል፡፡
የሶደሬ ጦጣዎችም ልክ የቦኩ ዘመዶቻቸው እንደሚያደርጉት ኑሯቸው የተመሠረተው በንጥቂያ ላይ ነው፡፡ የቦኩ ጦጣዎች ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ይርመሰመሳሉ፡፡ ዝንጀሮዎች ግን በአብዛኛው 4 እና 5 ሰዓት ላይ በብዛት ከወጡ በኋላ በ11 ሰዓት ወደ ሠፈራቸው ይከትታሉ፡፡
በነገራችን ላይ ዝንጀሮም ሆነ ጦጣ ከሰው የሚሻሉበትም መንገድ አለ፡፡ ቆየት ያለ አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው፤ ዝንጀሮ ከሕጋዊ ሚስቱ ውጭ ወደ ሌላ ሄዶ አይወሰልትም፡፡ ሚስቱ ብትሞትበትም ወይንም ሚስት ባል ቢሞትባት “ይመነኩሳሉ” እንጂ ሁለተኛ ጋብቻ አይፈጽሙም፡፡ ጦጣዎችም እንዲሁ ናቸው፡፡ ነውረኝነታቸው ግን በዚያ ሁሉ ሕዝብ መኻል የወንድና የሴት ግንኙነት መፈጸማቸው ነው።
ሌላው ወንድ ዝንጀሮ ሽንቱን ከሸና በኋላ ብልቱን በእጁ ይዞ ሽንቱን ማራገፉ ለንጽሕናው ያለውን ትኩረት ያመለክታል፡፡
በቦኩ ቆይታዬ አንድ ጅብ ከጧቱ 3 ሰዓት ገደማ አጠገባችን ጩኸቱን እንደ መድፍ ለቅቆ ቢያስደነግጠንም ግቢው በታጣቂዎች በሚገባ ስለሚጠበቅና አጥሩም የተጠናከረ በመሆኑ የፈራ ሰው አልነበረም፡፡ ይልቁንም ታካሚው ሁሉ እየሣቀ “አይ አጅሬ ጠብቶበት ሳይሆን ረፍዶበት ነው” አለ።


Published in ህብረተሰብ
Saturday, 02 May 2015 11:48

የፀሐፍት ጥግ

አዕምሮዬን ባዶ ለማድረግ ካልፃፍኩኝ አብዳለሁ፡፡
ሎርድ ባይረን
መፅሃፍ በውስጣችን እንደ አለት ረግቶ ለተጋገረው ባህር እንደመጥረቢያ ማገልገል አለበት፡፡
ፍራንዝ ካፍካ
ከምፅፈው ውስጥ ግማሹ ትርኪምርኪ ነው፡፡ ካልፃፍኩት ግን ጭንቅላቴ ውስጥ ይበሰብሳል፡፡
ጃሮድ ኪንትዝ
ብዙ ሰዎች ስለ መፃፍ ያወራሉ፡፡ ምስጢሩ ግን ማውራት ሳይሆን መፃፍ ነው
ጃኪ ኮሊንስ
በህይወት ውስጥ ሁሉም ነገር ለመፃፍ ተራ የሚጠብቅ ታሪክ ነው፡፡
ሜ.ጂ. ማርሽ
ፕሮፌሽናል ፀሐፊ፤ መፃፍ ያላቆመ አማተር ነው፡፡
ሪቻርድ ባች
 እንደምንፈልገው አን    ፅፍም፤ እንደምንችለው እንጂ፡፡
ሶመርሴት ሟም
መፅሐፉ አፍቃሪዎች ፈፅሞ ለብቻቸው ወደ መኝታቸው አይሄዱም፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
አሜሪካኖች ወፈር ያሉ መፃህፍትና ቀጠን ያሉ ሴቶች ይወዳሉ፡፡
ራስል ቤከር

Published in ጥበብ

   እንቅልፍ ከዓለም መሸሸጊያ ጥግ ነው፡፡ ከህይወት ተፋቶ፤ ከኑሮ ተለይቶ ሌላ ዓለም ውስጥ መግባት ነው፤ መተኛት፡፡
በእንቅልፍ ቡልኮ መጋረድ፣ ከዓለም ለተኳረፈ ምቹ ምሽግ ነው፡፡ ህይወት ጥልቅ ናት፤ በጥልቀትዋ ልክ መጥለቅና ከሁሉ በላይ መምጠቅን መታደል ቀላል አይደለም፡፡ ቀላል አይደለም ሳይሆን ከባድ ነው፡፡ ክብደቱ የሚሰማው ደግሞ ልብ ላይ ነው፡፡
መጥለቅና መምጠቅ የተለያዩ የሚመስሉ ነገር ግን ተመሳስሎን የታደሉ ቃላት (ወይም ሀሳቦች) ናቸው፡፡
ህይወት ጥልቅ ናት ብለናል፡፡ በህይወት ጥልቀት ልክ መጥለቅ ለሰው የሚቻል አይመስልም። የህይወት ጥልቀትዋና ርቀትዋ ሩቅ ነው፡፡ ወደ ህይወት ለመጥለቅ፣ በጥልቀት ተመልካችና አጥልቆና አርቆ አሳቢ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ውጫዊ ገፅታን ለማሳመር ቀለም መቀባባት እና የላይ የላይ ኑሮ መኖር ወይም የለብለብ ዕውቀት ባለቤት መሆን ህይወት ላይ አያነግስም፡፡ ህይወት ላይ ለመንገስ ህይወትን በጥልቀትና በርቀት መገንዘብ የተገባ ነው።
እርግጥ ነው ይህን ሳያደርጉ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሰው ወይም ስኬታማ መስለው የሚታዩ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የአጭር ርቀት ተጓዦች እንጂ ከህይወት ጋር በማይሎች የሚጓዙ አይደሉም፡፡ ከጥቂት ርቀት ጉዞ በኋላ ዘሎ ወራጆች ናቸው፡፡
ህይወት ጥልቅና ውስብስብ የሆነች፤ እንደ ዕጢ የጠጠረች፤ በተፈጥሮ ንጥረ ነገሮች የተሞላች ግዙፍ ክስተት ናት፡፡ ኑሮ አድካሚና ለቀቢፀ-ተስፋ የሚድር፣ በቀላሉ ግን የማይሰበር ወይም የማይሞነጫጨር አለት ነው፡፡
የህይወትን የመምጠቅ ዓይነት ወይም የምጥቀት ደረጃ ለመገንዘብ ምጡቅ (ጂኒየስ) መሆን ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ህይወት እንዲሁ ዝም ብላ መለስ ቀለስ የምትል፤ እንዲሁ ዝም ብላ የምትንጎራደድ ባልቴት አይደለችም፡፡ በርካታ ምርጫዎችን ከፊት ለፊታችን ታቀርብልናለች፡፡ የተሻለና የሚስማማኝ ነው የሚለውን መምረጥ የባለቤቱ ኃላፊነት ነው፡፡
ዓለም በተቃርኖ የተሞላች ናት፡፡ እያንዳንዱ ማንነት ወይም ክዋኔ አቻው የሆነ ሌላ ማንነት ወይም ክዋኔ አለው፡፡ ለወንድ ሴት፣ ለፀሐይ ዝናብ፣ ለመዓልት ሌሊት፣ ለብርሀን ጨለማ፣ ለህይወት ሞት፣ ለቅጥነት ውፍረት፣ ለርዝመት እጥረት፣ ለሀዘን ደስታ፣ ለለቅሶ ሳቅ … ወዘተ ….
ኑሮ ትግል ነው፡፡ እንደ በላይ ዘለቀ የበረታ፤ እንደ ማህተመ ጋንዲ ሰፊ ልቦና የታደለ፤ እንደ አብርሀም ሊንከን የፀና፤ እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ “በቃን!” ለማለት የደፈረ፤ እንደ ሶቅራጠስ በጥልቀት ያሰበ የሚረታው!
ያለበለዚያስ?!
ያለበዚያማ የሚሆነው ግልፅ ነው፡፡ ምርጫው ሁለት ነው፡፡ መርታት ወይም መረታት፡፡ መርታቱ ካልሰመረልን መርታት ዕጣ ፈንታችን ይሆናል፡፡ …
እውነት ነው፤ የኑሮ ጫና ከባድ ነው፡፡ እንደ ቀምበር ትከሻ የሚቆረቁር፤ እንደ ገጀራ አንገት የሚቀላ፤ እንደ ታቦት ስጋነ የሚያኮሰምን፤ እንደ ጅቡቲ በወበቅ የሚያፍን፤ እንደ ራስ ዳሽን ተራራ በቅዝቃዜ የሚያኮማትር ወዘተ …
የኑሮ ጫና ክብደት በቀላል ቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡ ጫናውን አጉልቶ አግዝፎ ለማሳየት የቃላት ኃይል ደካማ ነው፡፡
ለማንኛውም ህይወት እንዲህና እንዲያ ናት፡፡
* *  *
የሰው ልጅ ሸክላ ነው፡፡ በቀላሉ የሚሰነጠቅና በቀላሉ የሚሰበር! …
የየሰው ልጅ ሸክላ መሆኑን መረዳትና ለማስረዳት መሞከር ከንቱነትን መስበክ አይደለም። መሬት ላይ ያለውንና ስር የያዘውን እውነት ከመገንዘብ የሚመነጭ ራሱን የቻለ አንድ እውነት ነው፡፡ ሰው ሸክላ ነው ስል ተሰባሪ ነው ለማለት ብቻ አይደለም። ተሰባሪነቱ እንዳለ ሆኖ ከተሰበረ በኋላም በሌላ መልኩ ይሁን እንጂ ህልውናው መቀጠሉን ለመጥቀስ ጭምር ነው፡፡
በዕውቀቱ ስዩም እንዳለው ነው፡-
“ጋን ከጀርባ ወድቆ፣ ገል ሆኖ ቀጠለ
ከመሰበር ወድያም ሌላ ህላዌ አለ፡፡”
…ለመልማትም ለመጥፋትም መንገዱ ክፍት ነው፡፡ ማዕከላዊው ነገር ሰው ነው፡፡ ትልቁ ቁም ነገር ሰው መሆን ነው፡፡ ሰው ነን ካልን በኋላ ማንዴላን መሆንም ሆነ ሂትለርን መሆን የምርጫችን ጉዳይ ነው፡፡ ፈጣሪ ሰው አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ ፈጥሮ ግን አልጨረሰንም፡፡ ትንሽ ዕድልና መጠነኛ ድርሻ ለ‘ኛ ትቷል፡፡ ሰው አርጎ ከፈጠረን ወዲያ ሰናይ ወይም እኩይ የሚባለውን ማንነት ለመጎናፀፍ ምርጫው ያለው በእጃችን ነው፡፡ ማንዴላንም ሆነ ሂትለርን ሰው አድርጎ የፈጠረው ፈጣሪ ‘ራሱ ነው፡፡ ማንዴላን ማንዴላ፣ ሂትለርን ሂትለር ያደረገው ሰብዕና የተፈጠረው ግን በ ‘ራሳቸው (በማንዴላና በሂትለር) ነው፡፡
ሁለቱም የ‘ራሳቸውን የተለያየ መንገድ ተከትለዋል፡፡ ማንዴላ ሰናይ፤ ሂትለር እኩይ!...
ህይወት ፈተና ናት፡፡ ደካማውና ጠንካራው በወንፊት የሚጠለልባት!... የብርቱው ብርታትም ሆነ የለፈስፋሳ ሰው ደካማነት በሰፌድ የሚበጠርባት!..
ህይወት ፈተና ናት፡፡ ህይወት ጦር ሜዳ ናት፡፡ ህይወት ፈተናና ጦር ሜዳ በመሆንዋ ምክንያት ብቻ ሁለት አማራጭ እንደ ጅግራ ከፊታችን ይገተራል፡፡ ተኝቶ ማልቀስ ወይም በርትቶ መታኮስ!
ውጣ ውረድ ያዘለው፤ ወድቆ መነሳት ያጣመነው ማንነት ላይ እንደ በቆሎ የተዘራን፤ እንደ ዛፍ የበቀልን፤ እንደ ፅጌረዳ ያበብን ሰዎች ነን፡፡ (ፅጌረዳ ስል ከአበባው ጋር እሾህም መኖሩን ጠቆም አድርጎ ማለፍ መልካም ነው!)…
ትግል የህይወታችን አንዱ ክፍል ነው፡፡ በአካባቢያችን ከሚገኝ ደንቃራ ጋርም ሆነ ከ‘ራስ ጋር ሳይታገሉ ውሎ ማደር፤ አንግቶ ማምሸት፤ አምሽቶም ማንጋት፤ የሚቻል አይደለም፡፡ ደደቢት በረሀ ባንገባም፤ አሲምባ ተራራ ላይ ዳስ ባንጥልም፤ ሁላችንም ታጋዮች ነን፡፡ በህይወት ናቅፋ፣ በኑሮ ሳህል ላይ የተሰማራን ተራ ዜጎች ነን፡፡
“ተራ!” አልኩ?! … ተራ ምንድን ነው?
እውነት ለመናገር “ተራ” የሚባል ሰው የለም፡፡ ዜግነትም በተራነት የሚገለፅ ነገር አይደለም፡፡
ከፍታና ዝቅታ በህይወት ውስጥ የሚፈራረቅ ነገር ስለሆነ፣ ባንዱ ረክቶና ሰክኖ ለሁሌው የሚዘልቅ፤ በአንድ ቦታ ተረጋግጦ ስር ሰዶ የሚገኝ ፍጡር፤ ከፍጡርም ሰው አይገኝም፡፡
ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው፤ ሰው በመከራ ይፈተናል፡፡ ፈተና የሚጥላቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፤ በፈተና የሚሰሩ፣ በፈተና የሚፈጠሩ ሰዎችም አሉ፡፡ ስንዴ ፈካ፣ ፀዳ የሚለው ከተፈተገ በኋላ እንደሆነው ሁሉ፤ ከፈተናው በፊት ምንም የሆኑ ከፈተናው በኋላ ግን እንደ አዲስ፣ አዲስ ሆነው የሚፈጠሩ ሰዎች አሉ፡፡
መሰናክል ብልሀት ለመፍጠር አዕምሮአችንን እንድናሰራው ያደርገናል፡፡ የሰው አዕምሮ ደግሞ ረቂቅና መጢቅ አይደል?! ከደንቃራው ለማለፍ በምናደርገው መፍጨርጨር ብርታትን እንጎናፀፋለን፡፡ መሰናክልን እናሰናክላለን፡፡
በፈተና የተገነባ ሰውነት በቀላሉ አይዝልም። በፈተና ያደገና የጎለመሰ ተክለ-ሰብዕና በቀላሉ አይዘምም፡፡ በፈተና የታሸ ልብ በቀላሉ ሊወድቅ ወይም ሊመታና ሊረታ አይችልም፡፡
ህይወት የትግል መድረክ ናት፤ ተኝቶ ያለቀሰ ሳይሆን በርትቶ የተታኮሰ የሚነግስባትና ዘውድ የሚጭንባት ልዕልት!... ችግርን በመሸሽ ሳይሆን ፊት ለፊት ተጋፍጦ በማሸነፍ የማይነቃነቅ፣ ፅኑና ብርቱ ማንነትን ልንገነባ እንችላለን፡፡ ይገባልም፡፡
በርትተን ከተታኮስን ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም የግላችን ማድረግ እንችላለን፡፡
ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም የኛ ነው፡፡
በሮበርት ስቹለር ስንኞች ልሰናበት፡፡
“The sun is shining, the sky is blue!
There is a new day dawning for me and you.
With every dawning of the sun
New possibilities have just begun
With every breaking of the morn
Fresh opportunities are newly born.”

Published in ህብረተሰብ