Saturday, 02 May 2015 10:32

ጣት መቀሰር እስከመቼ?!

(ቆም ብሎ ማሰቡ ለራስም ለሀገርም ይጠቅማል!)

   “ህዝቡ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው፤ በሀገሪቱ ውስጥ ስራ አጥነት ተንሰራፍቶአል፤ መብራት፣ ውሃና ኔትወርክ የለም፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በትራንስፖርት ችግር እየተንገላቱ ነው፤ በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ፤ የግሉ ፕሬስ በነጻነት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ለመጥፋት ተቃርቦአል፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚፈለገው መልኩ በነጻነት መንቀሳቀስ አልቻሉም፤ በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን ለአደጋ በሚዳርግ መልኩ እየተሰደዱ ነው፡፡…” ሌሎችም ለቁጥር የሚታክቱ ምሬቶችና አቤቱታዎች ከየአቅጣጫው በየጊዜው ይሰማሉ፡፡ በዚችው በእኛዋ ሀገር፡፡
ከእነዚህ አቤቱታዎች አንዳንዶቹ መንግስትም ጭምር የሚቀበላቸው (የሚያምናቸው) ቢሆኑም እስካሁንም ድረስ ችግሮቹ መቀረፍ አልቻሉም፡፡ ለምን?! ምክንያቱ የሚመስለኝ የችግሮቹ መንስኤዎች ላይ አትኩሮ ችግሮቹን ለመቅረፍ ከመስራት ይልቅ ሰበብ መስጠት ወይም ጥፋቱን ተሸካሚ ፈልጎ በማሸከም ላይ ስለሚታትር ይመስለኛል፡፡ ሐጢአቱን ለሌሎች አሸክሞ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ፡፡
እስቲ ጥቂት ወደ ኋላ መለስ እንበልና ከላይ ለተነሱትና ለሌሎች አንዳንድ ችግሮች መንግስት ተጠያቂ ያደረገው እነማንን እንደሆነ እናስታውስ፡፡… በአጭሩ ለየትኛውም ችግር ራሱን ተጠያቂ አላደረገም ማለት ይቀላል፡፡ በተደጋጋሚ ችግሮቹን ከጉዳዮቹ ጋር እጅግ በጣም ጥቂት ንክኪ ያላቸው አካላት ላይ ጭኖ ራሱን “ነጻ አድርጎአል፡፡” አሁንም እየሆነ ያለው እንደዛ ይመስለኛል፡፡ ጊዜ ያለወጠው አዙሪት!
ዛሬም እንደ ቀድሞው መንግስትና ሚዲያዎቹ በደቡብ አፍሪካ፣ በሊቢያ በረሀና በሜዴትራንያን ባህር ዳርቻ ስደተኛ ወገኖቻችን በግፍ መገደላቸውን ተከትሎ ለችግሩና ለጥፋቱ ብቸኛ ተጠያቂ “ህገ ወጥ ደላሎች” (ቃሉ ራሱ የተጣራ ፍቺን ይሻል) ናቸው እያሉን ነው፡፡ ዘይገርም ነው! መቼ ይሆን ጣታችንን ሌሎች ላይ ብቻ መቀሰር የምናቆው?! መቼስ ነው ማድበስበሱን ትተን ከእውነታው ጋር መጋፈጥ የምንችለው?! ያሰኛል፡፡
ከምንጊዜውም በበለጠ መልኩ በአሁኑ ወቅት በርካታ ወገኖቻችን ህይወታቸውን ለአደጋ በሚዳርግ መንገድ ከሀገራቸው ተሰደዋል፤ እየተሰደዱም ነው፡፡ በመንገዳቸውም ሆነ ተሰደው በሚኖሩባቸው ሀገሮችም ህይታቸውን እስከሚያጡ ድረስ በርካታ እንግልቶች እየደረሱባቸው ነው፡፡ ይሄ ሀቅ ነው፡፡ የአለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የሠርክ ወሬ የሆነና እኛም የምንስማማበት ሀቅ፡፡ ታዲያ ጉዳዩ አቅጣጫውን መሳት የጀመረውና አለመተማመኑ የጎላው ዜጎቻችን የሚሰደዱበትን ምክንያት መጠየቅ ሲጀመር ነው፡፡ ያኔ ጉዳዩ ከመፍትሔው መነጠል ጀመረ፡፡ የሚመለከተውም ለዜጎቹ ኃላፊነት እንደሚሰማው አካል የችግሩን ምክንያቶች አምኖና ተቀብሎ በመጋፈጥ ችግሩን ከስሩ ለመቅረፍ ከመሞከር ይልቅ ችግሩ የሚሳበብበትን አካል መፈለግ ያዘ፡፡ የዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂ እከሌ ነው ለማለት፡፡ ያስገርማል፤ ያሳዝናልም!
እርግጥ ነው፡፡ ለአንድ ክስተት መፈጠር በርካታ ምክንቶች ሰበብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን እያንዳንዱ ምክንያቶች ምን ያህል ድርሻ አላቸው? የምክንያቶቹ መነሻስ (ሰበብ) ምንድን ነው? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ እውነታውን እስከፈለግን ድረስ ይህ ወደ እርግጡ ድምዳሜ የሚያደርሰን ጤናማ መንገድ ይመስለኛል፡፡…
እርግጥ ነው ሰዎች ከሀገራቸው እንዲሰደዱ “ህገ ወጥ ደላሎች” የሚያደርጉት የራሱ አስተዋጽኦ አለ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሌሎች ጭፍጫፊ ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መልካም፡፡… ቀጥለን ግን መጠየቅ ያለብን እነዚህ ምክንያቶች ለችግሩ የሚያዋጡት ድርሻ ምን ያህል ነው? የሚለውን ነው፡፡ መልሱ ብዙም ጥናትን የሚፈልግ አይደለም፡፡ ብዙም ሳንደክም ልንመልሰው እንችላለን፡፡ በመንግስት እየተጠቀሱ ያሉት ምክንያቶች በምንም መልኩ ለዜጎች መሰደድ በዋና ምክንያትነት ሊጠቀሱ ቀርቶ ስሌት ውስጥም የሚገቡ አይደሉም፡፡ ድርሻቸው ጥቂት ነውና፡፡
እውነቱን እንናገር ከተባለ፣ ወገኖቻችን እንዲሰደዱ ግፊት የሆኗቸው ሌሎች በዋናነት ሊጠቀሱ የሚገቡ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህን ምክንያቶች ለማወቅ የሚፈልግ አካል ካለ ተጓዦቹንና ከስደት ተመላሾቹን ቀረብ ብሎ ይጠይቃቸው፡፡ ሀገራቸውንና ወገኖቻቸውን ተለይተውና ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚሰደዱባቸውን ምክንያቶች ይነግሩታል፡፡…  ምክንያታቸው የኢኮኖሚ ችግር ነው፡፡ የእንጀራ ጥያቄ! ደግሞም ይህንን ማወቅ ውስብስብና የበዛ ምርምርን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሽሽቱንና ማድበስበሱን ስለፈለግነው እንጂ ለማንም ያልተደበቀ ያፈጠጠ ሀቅ ነው፡፡
አንዳንድ ነጥቦችን እያነሳን ጉዳዩን ለመመርመር እንሞክር፡፡ እስቲ በመንግስትና በሚዲያ ተቋማቱ “ፍረጃ” ተስማምተን፣ ለጥፋቱ ተጠያቂዎች “ህገ ወጥ ደላሎች ናቸው” ብለን እንነሳ፡፡ የምንደርስበት ውጤት (ብዙም ስሌት ውስጥ ሊገቡ የማይገቡ ሌሎች ጭፍጫፊ ሰበቦች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ) አሁንም የችግሩ ዋና ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እንዴት?
ሲጀመር ዜጎች የ“ህገ ወጥ ደላሎቹ”ን ስብከት ሰምተውና አምነው ከሆነ የሚሰደዱት፣ ደላሎቹ ጋር የወሰዳቸውም ሆነ ደላሎቹን እንዲያምኑ ያደረጋቸው ያለባቸው የኢኮኖሚ  ችግር ነው፡፡ የኢኮኖሚ ችግር ከሌለባቸውና የዳቦ ጥያቄያቸውን መመለስ የሚችሉ ከሆነማ ለምን ከደላሎቹ ጋር ይገናኛሉ? ለምንስ ደላሎቹ የሚሏቸውን ያምናሉ? መቼስ “መረጃው ስለሌላቸው ነው” የሚል የዋህ እንደማይኖር እገምታለሁ፡፡
ሀገር አቋርጠው ሲጓዙም ሆነ ደርሰው በሚኖሩባቸው ሀገሮች ህይወትን እስከማጣት የሚደርስ እንግልት ሊያገኛቸው እንደሚችል እኮ “ህገ ወጥ” ደላሎቹ “ታገኛላችሁ” ብለው ከሚሰብኳቸው በበለጠ መንግስትም ሆነ በርካታ መገናኛ ብዙሀን ያለማቋረጥ ነግረዋቸዋል፤ እየነገሩአቸውም ነው፡፡ ግን ከመሄድ አላመነቱም፡፡ ለምን? ማመን ስለማንፈለግ እንጂ መልሱ አሻሚ አይደለም፡፡ ይህንን የሚያጠነክር ሌላም ነጥብ እዚህ ጋ ማንሳት እንችላለን፡፡ በተሰደዱበት ሀገር ሲደርስባቸው ከነበረው እንግልት፣ ከሞት መንጋጋ አምልጠው… የመጡት ወገኖቻችንም ውለው ሳያድሩ አሁንም ተመልሰው ከሞት ወዳመለጡባቸው ሀገሮች እየሄዱ ነው፡፡ መቼም እጅግ የዋህ ካልሆንን በቀር “እነሱም በደላሎቹ ተታለው ነው” አንልም፡፡ አይተውታልና፡፡ ይኸው ነው፤ ማመን ቢገደንም ቅሉ በዚህም አልን በዚያ ዜጎቻችን ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ከሚሰደዱባቸው ምክንያቶች ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የኢኮኖሚ ችግር፣ የእንጀራ ጥያቄ… ነው፡፡ ይህንን ማመን ግን ተጠያቂ ስለሚያደርገን ሳይሆን አይቀርም፤ ሐጢአቱን ሁሉ ለደላሎች ሰጥተን ለመንጻት የምንሞክረው፡፡
ደግሞም እኮ (ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ትርፍ ካልሆነ በቀር) በደሉን የሚሸከም አካል ፈልገን እሱ ላይ ጣት መቀሰር በምንም ስሌት መፍትሔ አይደለም፡፡ መፍትሔው ስህተትንና ድክመትን አምኖ መቀበልና ችግሩን ፊት ለፊት መጋፈጥ ነው፡፡ በዚህም የችግሮቹ ምክንያቶች ላይ በማተኮር መስራት ነው ለሀገርም ለራስም የሚጠቅመው፡፡ ችግሩን ሌሎች ላይ ስላንከባለልንና ጣታችንን ስለቀሰርን ወይም ጉዳዩ ሌላ አቅጣጫና ትርጉም እንዲይዝ ስለደከምን “ነጻ” የምንሆን ይመስለናል እንጂ አንሆንም፡፡ ይህንንም በተደጋጋሚ አይተነዋል፡፡ እያየነውም ነው፡፡
የትናንት ቀመር ለትናንት እንጂ ለዛሬ አይሰምርም፡፡ ይህ ዘመን ሌላ ነው፡፡ የህዝቡ አስተሳሰብም ሆነ እውቀት የቀድሞው አይደለም፡፡ ተለውጦአል፤ አድጓልም”፡፡ ያልነውንና የሰጠነውን ብቻ የሚያምንበትና የሚቀበልበት ዘመን አልፎአል፡፡ ስለ ሁሉም ነገር ምናልባትም ከምንነግረው በላይ ያውቃል፡፡ ስለ ሁሉም መረጃ አለው፡፡ ለቴክኖሎጂው ምስጋና ይግባውና ትውልዱ መረጃን በእጁና በኪሱ ይዞ ነው የሚዞረው፡፡ ለዚህም ነው በአዎንታም ይሁን በአሉታ ለየክስተቱ ምላሽ ሲሰጥ የሚስተዋለው፡፡ ይህንን ማወቅና መገንዘብ፣ ተገንዝቦም ራስን ከትውልድና ከሁኔታዎች ጋር ማዘመን ከአንድ መንግስት የሚጠበቅ ብልህነት ነው፡፡ ቆም ብሎ ማሰቡ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግስት… ይጠቅማል፡፡
በተለይ አሁን ከምንጊዜውም በላይ ሀገራችንና ዜጎቿ በየአቅጣጫው እየተፈተኑ ያሉበት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ሀገሩንና ህዝቦቿን እወዳለሁ የሚል ዜጋም ሆነ መንግስት ዛሬ ትናንት እንዳልሆነ ሊያስተውል፣ ቆም ብሎም ሊያስብ ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ለሁሉም ይጠቅማልና፡፡… በተለይ መንግስት ከተለመደው አዙሪት መውጣት፣ ኃላፊነት መውሰድና ከችግሮች ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ ይኖርበታል፡፡ እስከፈለገ ድረስ ይህንን ማድረግ አያቅትም፡፡ ሥራን መስራት፣ ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ሁሌም ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግና ጣትን መቀሰር ራስን ለትዝብት ከመዳረግ ባለፈ አንዳች ትርፍ የለውም፡፡ ደጃፍን እንጂ ወንዝ አያሻግርም፡፡  
አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር እውነቱን አምኖና ተጋፍጦ ዘላቂ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ ጣት የምንቀስርበትን መፈለግ ለጊዜው የሚበጅ ቢመስለንም የነገ እጥፍ ኪሳራ ነው፡፡ ደግሞም እኮ ድክመትን መቀበል ጀግንነት እንጂ ሽንፈትና ክስረት አይደለም፡፡ አያስከፋምም፡፡ የሚያስከፋውስ ችግሮችን ሌሎች ላይ መጣል፣ ለማድበስበስ መሞከርና ችግሩን ላልተገባ የፖለቲካ ትርፍ ለማዋል መድከም ነው፡፡
ደግሞም እንደ መንግስት በዚህ ሂደት ውስጥ የምናደርጋት እያንዳንዷ ክንውን፣ የዛሬ አንድምታዋንና ነገ የምታፈራውን ፍሬ መገመት ይገባል፡፡ እስከ ዛሬ የዘራነው ምን እንዳፈራልን እያየን ነው፡፡ ዛሬ የምንዘራውም ነገ ልጆቻችንን ሊያጠፋ እንደሚችል እንገንዘብ፡፡ ፊታችን ስለቆመው ዛሬ ብቻ ሳይሆን ስለነገም ቆም ብለን እናስብ፡፡ ደግሞም የምር ከፈለግን አያቅተንም፡፡ በፍጹም!
መልካም ሰንበት!

የሰሞኑ አሳዛኝ ክስተት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን አንድ ሊያደርግ ይችላል፤ ነገር ግን በሃገሪቱ ተመዘገበ በተባለው ተአምራዊ ኢኮኖሚ ላይ ግን ጥርጣሬን ያጭራል?”    ረዳት ፕሮፌሰር ሃሰን ሁሴን

በአንድ ሳምንት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ተደራራቢ የሞት መርዶን አስተናግደዋል፡፡ ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም በሊቢያ የሚንቀሳቀሰው የእስላማዊ መንግስት አቀንቃኙ አይኤስ፣ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን መግደሉን አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በአይኤስ እጅ የወደቁት ደግሞ የተሻለ ህይወት ፍለጋ በሊቢያ አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ባደረጉት ጥረት መሃል ነው፡፡
ይህ አስከፊ አጋጣሚ የተፈጠረውም በዚያው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ በስደት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ባለበትና 3 ኢትዮጵያውያን የመገደላቸው መርዶ በተነገረበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ ለኢትዮጵያውያን መራር ያደርገዋል፡፡
በሌላ በኩል አልጀዚራም ሆነ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፤ በየመን እንዲሁ በተመሳሳይ ስደት ላይ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በጦርነት መሃል ለሰቆቃ ተዳርገዋል፡፡ በዚያው አስከፊ ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው ሮቤ ከተማ እና አካባቢው የሚገኙ ወላጆች፣ ሚያዚያ 11 ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ከ900 በላይ ስደተኞች ጭና ስትገጓዝ የነበረችው ጀልባ መስጠሟን ሰምተው መሪር ሃዘንን አስተናግደዋል፡፡
በአንድ ሳምንት ውስጥ የተፈጠሩት እነዚህ ሁሉ አሳዛኝ ክስተቶች፣ለጊዜው ኢትዮጵያውያንን አንድ ያደረጉ ቢመስልም በዚያው ልክ ኢትዮጵያውያኑን ከአስፈሪ ሞት ጋር ለመጋፈጥ ለምን ስደትን የመጀመሪያ ምርጫቸው ያደርጋሉ የሚለው በሁሉም ህሊና ውስጥ የሚመላለስ ጥያቄ ሆኗል፡፡
ቀውሱ የተፈጠረው የኤስያ ነብሮች የተባሉ ሃገራት በ1970ዎቹ ያስመዘገቡት አይነት ተአምራዊ ኢኮኖሚ ሃገሪቱ አስመዝግለች በሚባልበትና የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ማጠናቀቂያ ዓመት ላይ መሆኑ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊነትን እየተላበሰች ነው በተባለባት ሀገር መሆኑ ነገሩን ይበልጥ አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ በተደጋጋሚም ሃገሪቱ ከአፍሪካ ሃገሮች ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች ነው ከተባለ ለምንድነው በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶቿና ሴት ልጆቿ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሃገራቸውን ጥለው የሚሰደዱት? መቼስ ነው ይሄ ፍልሰት የሚያበቃው?
እንደሚታወቀው አስደንጋጩ ዜና ከተሰማ በኋላ የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ “ክስተቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ላሰቡ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ነው” ብለዋል፤ ግን የሃገሪቱ ወጣቶች እንደ ማስጠንቀቂያ አላዩትም፡፡ በአገራቸው የተሻለ ህይወት የመኖር ህልም ያላቸው አይመስልም፡፡ በሃገሪቱ ከፍተኛ ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መበራከት፣የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እድል----ከፖለቲካ ጋር መያያዙና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን የፓርቲ አባልነት መስፈርት ማስፈለጉ፣ ከፍልሰቱ ጀርባ እንዳለ በርካታ እማኞች ይገልጻሉ፡፡
መቀመጫውን ለንደን ያደረገው አለማቀፉ የእድገት ማዕከል፤ በ2012 እ.ኤ.አ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በከተማ የሥራ አጥነቱ በከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣
ማስማ በገጠርም ወጣቱ መሬት አልባ መሆኑን ጠቃሚ የስራ እድሎ እንደሌሉት ጠቁሟል፡፡ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው፤በሃገሪቱ በሚታይ ደረጃ የትምህርት አቅርቦት ቢጨምርም ተምሮ ለሚወጣው ዜጋ በተማረበት የሙያ መስክ በቂ የስራ እድል አለመኖሩን አስቀምጧል፡፡
በአይኤስ ከተገደሉት መካከልም በዲግሪ የተመረቁ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ ሳውዲ አረቢያ ከ100ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ባስወጣችበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱም የአይኤስ ሰለባ ሆነዋል፡፡ እንዲሁ በሃገሪቱ ካሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በጥሩ ደመወዝ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረ ወጣትም አለበት፡፡
ይሄ ሁሉ የሚያመለክተን ብዙ የሚወራለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ የሃገሪቱን ወጣትና የህዝብ ቁጥር ምጣኔን ለማስተናገድ አለመብቃቱን ነው፡፡ የሀገሪቱን ወጣቶች ለስደት የሚዳርገው የኢኮኖሚ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ወጣቶች አማራጭ የመረጃ ምንጭ መከልከላቸውና የነፃነት ስሜት እንዳይሰማቸው መደረጉ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በየአገሩ የሚገኝ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂ ነው፡፡ በየመን 75ሺህ ያህል የተመዘገቡ ስደተኞች መኖራቸውን የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት የጠቆመ ሲሆን በኬንያ ከ20 ሺህ በላይ፣ በግብፅና በሶማሊያ ወደ 3ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በስደተኝነት ተመዝግበዋል፡፡
አገሪቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች በግንቦት ወር ምርጫ ይደረጋል፡፡ ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄድ ምርጫ ቢሆንም ላለፉት 10 ዓመታት ገዥው ፓርቲ፣ የፀረ ሽብር ህግና የሲቪል ማህበራት ህግ በማውጣት እንዲሁም ተቃዋሚዎችን በተለያዩ መንገዶች በማዳከም፣የምርጫ መወዳደሪያ ሜዳውን መዝጋቱም በገሃድ የሚታይ ሆኗል፡፡
ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን በማፈን ደግሞ አገሪቱ ከአለም በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ጋዜጠኞችን በማሰርም ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ገዥው ፓርቲ መገናኛ ብዙሃንን በሙሉ ተቆጣጥሯል፡፡ እንዲያም ሆኖ አሁን ባለው ሁኔታ ጥቂት ተቃዋሚዎች በቀጣዩ ምርጫ ፓርላማ ሊገቡ ይችሉ ይሆናል፤ ወጣቶች ግን አሁንም የፖለቲካ ተሳትፏቸው የተገደበ ነው፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ውስብስብ ችግሮች ባሻገር ኢትዮጵያ በአካባቢው ከሚገኙት ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ አንፃር የተረጋጋች ሃገር ነች ማለት ይቻላል፡፡ የአገሪቱ መንግስት በሽብርተኝነት ላይ ጦርነት አውጃለሁ ማለቱ ደግሞ የአሜሪካን ቀልብ ገዝቷል፡፡ ይሄም አሜሪካን የመሳሰሉ ለጋሽ ሃገራት ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ነፃነታቸውን እንዲያገኙ ግፊት ከማድረግ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል፡፡ በሃገሪቱ ያለው የጎሳና የሃይማኖት ግጭት፣ የፖለቲካ ነፃነት እጦት በሃያላኑ ሃገራት እምብዛም ትኩረት የተሰጠው አይመስልም፡፡ ዜጎቿን በስደት እያጣች ያለችው ሃገር፣ ይበልጥ በአካባቢው በሽብርተኝነትና ደህንነት ላይ ብቻ አተኩራ የምትቀጥል ከሆነ፣የዜጎች ፍልሰትና የማህበራዊ አለመረጋጋቱም በዚያው መጠን ይቀጥላል፡፡ ከዚያ ይልቅ የቅርብ ጊዜውን አሳዛኝ ክስተት መነሻ በማድረግ መንግስት የመፍትሄ ሃሳቦችን መፈለግ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ቀደም የታለፈባቸውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ቁጭ ብሎ በመመርመር፣ሁነኛ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ካልተቀመጡ አሁንም ስደቱ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያውያንም አሳዛኝና አስደንጋጭ መርዶዎችን መስማታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ ረዳት ፕ/ር ሀሰን ሁሴን፤ በአሜሪካ ሚኒሶታ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡
 ፅሁፉ ሚያዚያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም በአልጀዚራ ድረ-ገፅ ላይ ታትሞ ለዓለም የተሰራጨ ነው፡፡  
*ከላይ በቀረበው ጽሁፍ ውስጥ የተካተቱት ሃሳቦች በሙሉ የጸሃፊው ብቻ ነው፡፡

Published in ዜና

    “ሁላችንም በፍርሐት ውስጥ እንድንገባ አደረጉን፡፡ ግርፋቱንና ስቃዩን በአይኔ ባላየውም ጩኸቱን ግን እሰማው ነበር፡፡”
ባለፈው አመት ሚያዝያ ላይ ነበር ሙምባይ ውስጥ በሚገኝ የኬሚካል ኩባንያ አማካኝነት የባህር ሐይል ኦፊሰር ለመሆን ስልጠና የወሰድኩት። ስራችንን ለመጀመር ወደ መርከቧ የተሳፈርነው ሰዎች እኔን ጨምሮ 22 ነበርን፡፡ ከህንድ የተውጣጡ ፕሮፌሽናል መርከበኞች እና ኢንጂነሮች ይገኙበታል። መርከቧ ላይ ከተሳፈርነው ሰዎች መካከል በእድሜ ትንሹ እኔ ነበርኩ፡፡ 21 ዓመቴ ነው፡፡
መርከባችን የተነሳችው ከህንድ ሲሆን አቅጣጫዋ ደግሞ ወደ ኖርዌይ ነበር፡፡ ጉዞው 25 ቀናቶችን ይወስዳል፡፡ ጉዞ በጀመርን በአራተኛው ቀን ላይ አንድ ባልደረባችን ከፊት ለፊታችን የምትመጣውን ጀልባ ተመልክቶ ጩኸቱን አቀለጠው፡፡ ከኦማን 120 ማይል በሚርቅ ባህር ላይ ነበርን፡፡ ይህ ክልል ደግሞ አደገኛና አስፈሪ ነው፡፡ የጀልባዋን አመጣጥና መጠን ተመልክተን ዘራፊዎች መሆናቸውን አወቅን፡፡
ወዲያውኑ ህንድ ውስጥ ላለው የባህር ሐይል ጣቢያ የሬዲዮ ግንኙነት አደረግሁኝ፡፡ ነገር ግን ዘግይቼ ነበር፡፡ በደቂቃዎች ውስጥ ስድስት የባህር ዘራፊዎች መርከባችን ላይ በመንጠላጠል የጥይት እሩምታ ከፈቱብን፡፡ በጣም አስፈሪና አስደንጋጭ ነበር፡፡ እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አልነበረንም።
ወዲያውኑ በቀማኞቹ እየተገፈተርን ወደ ሞተር መቆጣጠሪያው ክፍል ውስጥ ገባን፡፡ ወለሉ ላይ በደረታችን እንድንተኛ ታዘዝን፡፡ ዘራፊዎቹ ለምንሰራለት ኩባንያ የ15 ሚሊዮን ዶላር ጥያቄ እንደሚያቀርቡና ገንዘቡን ካላገኙ እንደሚገድሉን በተሰባበረ እንግሊዝኛ ደነፉብን፡፡  ከፍተኛ ፍርሐት ዋጠን፡፡ እስከ ቀጣዩ ጧት ድረስ ሁላችንም ከተኛንበት ወለል ላይ ሳንንቀሳቀስ በዝምታ አሳለፍን፡፡ ሌሎች 6 ዘራፊዎች መርከባችንን ከተቀላቀሉ በኋላ ወደ ሶማሊያ ሊወስዱን እንደሆነ ነገሩን፡፡
በመርከብ ላይ ታፍነን ያሳለፍነው አስቸጋሪ ህይወት እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አልነበረም፡፡ በመቆጣጠሪያው ክፍል ውስጥ በየጥጉ ኩርምት ብለን ተቀምጠናል፡፡ መስኮት የሌለው ክፍል በመሆኑ የታፈነ አየር ለመሳብ ተገደናል፡፡ መፀዳጃ ቤት እንድንጠቀም ቢፈቀድልንም ተበላሽቶ በመጥፎ ጠረን ታውዷል፡፡ በዚህ ምክንያት ሁላችንም ታመምን፡፡ ምግብ የሚሰጠን በሳምንት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እሱም ህይወታችንን ለማቆየት እንዲረዳን ያህል ከድንች እና ሽንኩርት የተሰራ ነበር። በኋላ ላይ እግራችንን እንድንዘረጋ ስለፈቀዱልን ትንሽ ተንፈስ አልን፡፡
ዘራፊዎቹ የደቀኑብን ጠብመንጃ የማምለጥ ተስፋችንን ገድሎታል፡፡ ከነሱ ጋር ወዳጅነት እንዳንፈጥር ደግሞ ዘወትር ያስፈራሩናል፣ ይደበድቡናል፡፡ በኔ ላይ መጥፎ ድብደባ እንዳይደርስብኝ የተቻለኝን ባደርግም ባልደረቦቼ ግን ክፉኛ ሲቀጠቀጡና ሲሰቃዩ ተመልክቼያለሁ። አንደኛውን ባልደረባዬን በኤሌክትሪክ አሰቃይተውታል፤ ሌላኛውን ደግሞ ከብረት ጋር ጠፍረው በማሰር ለረዥም ሰዓት ደብድበውታል። በሌላኛው ክፍል ውስጥ የነበሩ ወዳጆቼ እንደሚሰቃዩ በድምፃቸው አረጋግጫለሁ፡፡ አሁን ድረስ የስቃይ ድምፃቸው ያቃጭልብኛል፡፡ እኔን ልክ እንደ ሌሎቹ ባልደረቦቼ ለምን ብዙ እንዳላሰቃዩኝ አላውቅም፡፡ ምን አልባት ገና ለጋ አልያም የማልጠቅም መሆኔን ተረድተው ይሆናል።
አንዳንድ ባልደረቦቼ ከዘራፊዎቹ ጋር ይፋጠጡ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን ከእንዲህ መሰሉ ነገር እጠነቀቅ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ጧት፤ ከተኛሁበት የብረት ወለል ላይ ስነቃ በዚያው ቀን እንድሞት እመኝ ነበር። ወዲያው ደግሞ ራሴን በማረጋጋት የወደፊቱን ለማየት እቅበጠበጣለሁ፡፡ ማድረግ የቻልኩት ግን ዝም ብዬ መጠበቅ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ከመካከላችን ውስጥ አንደኛችንን መርጠው ህንድ ለሚገኘው ኩባንያችን እንድንደውል ያደርጉ ነበር፡፡ እኛም በተሰጠን የስልክ እድል ተጠቅመን ህይወታችንን እንዲታደጉልን የኩባንያ ሰዎቻችንን እንማፀናለን፡፡ እነሱ ግን የገንዘቡ መጠን እስካልተቀነሰላቸው ድረስ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ይነግሩናል፡፡
በመጀመሪያዎቹ አራት ወራቶች ውስጥ፤ በወር አንድ ጊዜ ከቤተሰቦቻችን ጋር በስልክ እንድንገናኝ ተፈቀደልን፡፡ ዘራፊዎቹ ይህን ያደረጉት ቤተሰቦቻችን ኩባንያ ላይ ግፊት እንዲያደርጉ ነበር። ነገር ግን ከቤተሰቦቻችን ጋር ገና ጥቂት ቃላቶችን ብቻ እንደተለዋወጥን ስልኩን ይነጥቁናል፡፡ ከስልኩ መቋረጥ ጋር የኛም አንጀት አብሮ ይቆረጣል፡፡
ገንዘቡ ሳይከፈል ብዙ ወራቶች ካለፉ በኋላ ዘራፊዎቹ ካፒቴናችንን ወስደው በሌላ ጀልባ ለብቻው አስቀመጡት፡፡ ይገድሉታል በሚል ሁላችንም ጭንቀት ውስጥ ገባን፡፡ እነሱ ግን ኩባንያው የተጠየቀውን ገንዘብ እንዲከፍል አሁንም የበለጠ እንድንለምን ነገሩን፡፡ ከ238 ቀናቶች በኋላ፣ እንድናለን ብለን ባልገመትንበት ሰዓት ኩባንያችን አምስት ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ፡፡ የጀርመን መርከብ ሊወስደን እንደሚመጣም ተነገረን፡፡ ዘራፊዎቹ ገንዘባቸውን ካገኙ በኋላ ሌላ ጀልባ ላይ ተሳፍረው ከአካባቢው ጠፉ፡፡ የተባለችው የጀርመን መርከብ መጥታ ስትወስደን ደስታዬ ወደር አልነበረውም፡፡ ከ238 ቀናት በኋላ አይኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ብርሐን አየ፡፡ ደንዝዤ ስለነበረ አላለቀስኩም፡፡ ሌሎቹ ግን እየነፈረቁ ነበር፡፡ ለቅሷቸውን መቆጣጠር አልቻሉም፡፡ እኔ እንደገና የተወለድኩ ያህል ነበር የተሰማኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ የበላሁት ምግብ፣ የወሰድኩት ሻወር፣ የቀየርኩት ልብስ ሁሉ ለኔ የማይታመን እንግዳ ነገር ነበር፡፡ ከስድስት ቀናት በኋላ ቤተሰቦቼ ጋር ተቀላቀልኩ። ሰውነቴ ከመክሳቱ በተጨማሪ ሁለመናዬ አስቀያሚ ሆኗል፡፡ ይህን ጉስቁልናዬን የተመለከቱት ቤተሰቦቼ በጣም አለቀሱ፡፡ ወደተከራየሁት መኖሪያ እንደተመለስኩ መርከብ ላይ በተፈጠረብኝ አጠቃላይ ሁኔታ ንዴቴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም አይነት ህክምና ለመውሰድ አልፈለግሁም፡፡ በህይወቴ ውስጥ የተፈጠረው ይህ አስቀያሚ አጋጣሚ ስራዬን እንድተው አላደረገኝም፡፡ እንዲያውም ተጨማሪ የመርከበኝነት ስልጠና ከወሰድኩ በኋላ እንደገና ወደ ባህር ስራዬ ተመለስኩ፡፡ ዘራፊዎቹ የህይወቴን አቅጣጫ እንዲቀይሩት አላደረግሁም፡፡ ጉዳቱን እንደሆነ አንዴ ቀምሼዋለሁ፤ ከዚህ በላይ ምኔን ይጉዱት?
(ዲፔንድራ ይሀንን ታሪኩን በራሱ ድምፅ ቀርፆ በኢንተርኔት ለቆታል፡፡)   

Published in ዜና

198 ሜትር ይረዝማል፣ 46 ወለሎች ይኖሩታል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት በእርዝማኔው ቀዳሚ እንደሚሆን የተነገረለትን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ በአዲስ አበባ ከተማ ለማስገንባት ከቻይናው የኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲኤስሲኢሲ) ጋር ስምምነት መፈጸሙን ዥንዋ ዘገበ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በአዲስ አበባ በተከናወነው የፊርማ ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ፣ 198 ሜትር ርዝመትና 46 ወለሎች የሚኖረው የወደፊቱ የባንኩ ዋና ጽ/ቤት፣ በእርዝማኔው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ጥራቱም ከአፍሪካ ምርጥ ህንጻዎች አንዱ እንደሚሆን እናምናለን ብለዋል፡፡
ህንጻውን የሚገነባው የቻይናው የኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲኤስሲኢሲ የኢትዮጵያ ቅርንቻፍ ጄኔራል ማናጀር ሶንግ ሱዶንግ በበኩላቸው፣ ኩባንያው በቻይና መሰል ግዙፍ የህንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በስኬታማ ሁኔታ ሲያከናውን እንደቆየ አስታውሰው፣ ህንጻው ለቻይና እና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካም አዲስ ገጽታን የሚያላብስ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ኩባንያውና ባንኩ በቀጣይ በጋራ ተረባርበው ፕሮጀክቱን ስኬታማ በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያረጋግጡም ገልጸዋል፡፡

Published in ዜና

   ታዋቂዎቹ ድምፃዊያን ነዋይ ደበበ እና ጎሳዬ ተስፋዬ በሊቢያ አሰቃቂ ግድያ ለተፈፀመባቸው   ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት መታሰቢያ የሚሆኑ ዜማዎችን እንደሰሩ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ኢትዮጵያውያን ለገጠማቸው ብሄራዊ ሃዘን ከማንም በላይ የጥበብ ሰዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ያለው ነዋይ፤ ህዝቡ አንደበታችን ብሎ የጥበብ ሰዎችን ስለሚወክል እኔም  የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለመግለፅ ሙዚቃውን ሰርቻለሁ ብሏል፡፡ “በኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ የተፈፀመው ግፍ መቆም አለበት ብለን ዛሬ ካልወሰንን ነገ የባሰ እንዳይመጣ ያሰጋኛል” ያለው ድምፃዊ፤ ሙዚቃውን ህዝቡን ለማፅናናትና መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሰራው ተናግሯል፡፡
“ሁሉም ያልፋል እስኪያልፍ ግን ያለፋል” በሚል ስያሜ የሰራሁት ሙዚቃ እንደ መዝሙር ሊታይ የሚችልና ዜማዊ ማስተማሪያ የሚሆን ነው ያለው ድምፃዊው፤ ግጥምና ዜማውን ራሱ እንደሰራው ገልፆ ሙዚቃውን ያቀናበረለት ወደፊት በሚያወጣው አልበሙ ከአምስት በላይ ዘፈኖችን የሰራለት ታምራት አማረ በቀና እንደሆነ ገልጿል፡፡ ሙዚቃው ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች መሰማት እንደጀመረ ጠቁሞ፤ ለሙዚቃው ክሊፕ ለመስራት በሳምሶን ስቱዲዮ በኩል እየተንቀሳቀስን ነው ብሏል፡፡  
እንዲህ ያለ መሪር ሀዘን ሲያጋጥም ቅስም ይሰብራል ያለው ጐሳዬ በበኩሉ፤ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመው ግፍ ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ ተሰምቶኝ የማያውቅ ጥልቅ ሀዘን ፈጥሮብኛል ብሏል፡፡ ሀዘኑን የሰማሁት አዳዲስ ስራዎችን እያዘጋጀሁ ባለሁበት ሰዓት ነው ያለው ጎሳዬ፤ እንደ ድምፃዊነቴ ሀዘኔን የምገልፀው በጉሮሮዬ በመሆኑ “አኬልዳማ” የሚል የመታሰቢያ ሙዚቃ ሰርቻለሁ ብሏል፡፡ አገሪቱን በገጠማት ሀዘን ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ደም ያላቸው የዓለም ህዝቦች ሁሉ ክፉኛ ማዘናቸው ልቤን ነክቶታል ያለው ወጣቱ ድምፃዊ፤ በሙያው ያለውን ለማበርከት ማቀንቀኑን ተናግሯል፡፡
የመታሰቢያ ሙዚቃውን ግጥም፣ ዜማና ቅንብር የሰራው መኮንን ለማ (ዶክተሬ) እንደሆነ የገለፀው ጎሳዬ፤ ጌታቸው ኃይለማርያም አብሮት እንደተጫወተ፣ አሌክስ ባሪያው ደግሞ ካጀቡት ድምፃዊያን አንዱ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
 የጎሳዬ “አኬልዳማ” ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች እየተሰማ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በድሬደዋ የጎርፍ አደጋ ባጋጠመበት ወቅት የመታሰቢያ ሙዚቃ ሰርቼ ነበር ሲል ያስታወሰው ጎሳዬ፤ ማህበራዊ ሃላፊነቴን ለመወጣት ምንጊዜም ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ጎን እቆማለሁ ብሏል፡፡       

Published in ዜና

    የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ባለፈው ዓመት ሐምሌ መጨረሻ ላይ ጀምሮ ያቋረጠውን 8400 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ሎተሪ (SMS) ከነገ አንስቶ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
ሎተሪው በየቀኑ የሚበረከቱ የሳምሰንግ ሞባይሎች፣ በየሳምንቱ የሚበረከቱ ቶሺባ ላፕቶፖችና 21 ፍላት ስክሪን ቲቪዎች ሲኖሩት፣ በየ15 ቀኑ የሚወጡ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ ሞተር ሳይክሎችና ፍሪጆች እንዳሉት ማህበሩ አስታውቋል፡፡ በሎተሪው መሃልና መጨረሻ ላይ የሚወጡ መኪኖችም እንደተዘጋጁ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከሎተሪው ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በቀጥታ ማህበሩ ለጀመረው የኢ.ሴ ማዕከል ማሰሪያ የሚውል ሲሆን ማዕከሉ ለስብሰባዎችና ስልጠናዎች የሚያገለግሉ አዳራሾች፣ የቢሮ ክፍሎች፣ የሚከራዩ አዳራሾች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ ከኪራይ የሚገኘው ገቢ ለጥቃት ሰለባዎችና በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሴቶች ድጋፍ ማድረግያ እንዲሁም ማህበሩ በገንዘብ ራሱን እንዲችል ያግዛል ተብሏል፡፡
ባለፈው ዓመት ሐምሌ መጨረሻ ላይ የተጀመረው የማህበሩ 8400 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ሎተሪ ከ15 ቀናት በኋላ የተቋረጠው የ8100 የህዳሴ ግድብ SMS ሎተሪ በመጀመሩና ሁለቱን መልዕክቶች በአንዴ ማስተላለፍ ስለማይቻል ነበር ያለው ማህበሩ፤ ከነገ አንስቶ የሚጀመረው የ8400 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ሎተሪ ለ3 ወራት ይቀጥላል ብሏል፡፡

Published in ዜና

     ለምርጫ ቅስቀሳ ባልተፈቀዱ ቦታዎች ላይ ፖስተር ለጥፏል በሚል ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስጠንቀቂያ የደረሰው ሠማያዊ ፓርቲ፤ ድርጊቱ በሌላ አካል እንደተፈፀመና የፈፀመውን አካል ምርጫ ቦርድ አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድለት ጠየቀ፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት ምርጫ ቦርድ የፓርቲው ፖስተሮች በእምነት ተቋማትና ት/ቤቶች አካባቢ ተለጥፈው መገኘታቸውን መግለፁ ትክክል ነው፤ ፓርቲያቸው በማያውቀው መልኩ ተለጥፈው የተገኙ በመሆናቸው ቦርዱ ለጣፊውን አካል አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለቦርዱ አስገብተዋል፡፡
የፓርቲው የቅስቀሳ ፖስተሮችም እየተቀደዱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዮናታን፤ ፓርቲው ቅስቀሳ በሚያደርግባቸው አካባቢዎች ጭምር የቅስቀሳ ፖስተሮቹ የእምነት ተቋማት ላይ ተለጥፈው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱን ሊፈጽም የሚችል የተደራጀ ቡድን ሊኖር እንደሚችልም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት አይኤስንና ሽብርተኝነትን ለማውገዝ በጠራው ሠልፍ ላይ ለተፈጠረው ሁከትና ግርግር ሠማያዊ ፓርቲን ተጠያቂ ማድረጉን የተቃወመው ፓርቲው፤ የመንግስት ውንጀላ የሚቀጥል ከሆነ መንግስትን፣ ፌደራል ፖሊስንና የሃሠት ወሬዎችን እያሠራጨ የፓርቲውን ስም እያጐደፈ ነው ያለውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ለመክሰስ እንደሚገደድ አስታውቋል፡፡

Published in ዜና
Page 19 of 19