Saturday, 30 May 2015 11:48

ፖንሴት እና ጎንደር

 

 

 

“አፄ ኢያሱ፤ የመድሓኒት ቅመማውን እንዳሳየው ይፈልጋል፡፡ መድሐኒቶቹ የሚያስከትሉትንም ውጤት ለማወቅ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ በዚህ ሳይወሰን ወደፊት መድሐኒቶቹን ለመሥራት እንዲቻል የአሰራር ሂደቱን በሰነድ እንድመዘግብለት ይጠይቀኝ ነበር፡፡--”

ጨዋራችንን ከነበረበት አንስተን አንቀጥል፡፡

እንደ ፖንሴት ገለፃ፤ በጎንደር ቤተመንግስት ግቢ አራት አብያተ ክርስትያናት አሉ፡፡ በእነዚህ አራት ቤተክርስትያናት የሚያገለግሉ መቶ የሚሆኑ ካህናት እንዳሉ የሚገልፀው ፖንሴት፤ ‹‹እኒህ ካህናት የቤተመንግስት ሠራተኞችን የመፅሐፍ ቅዱስ ንባብ ያስተምራሉ›› ይላል፡፡ ፖንሴት፤ ጎንደርን ያን ያህል ውብ ከተማ ሆና አላገኛትም፡፡ ‹‹በእርግጥ›› ይላል ዶ/ር ፖንሴት፤‹‹ከመሐል ተነስቶ በ14 ወይም በ19 ከ.ሜ መጠነ ዙሪያ፤ትልቅ ከተማ ለማለት የሚያስችል ሁኔታ አላት›› (At three or four leagues in circumference, it was big enough, to be sure)፡፡

እንደ ፖንሴት ገለፃ፤ ከቤት አሰራር (አርክቴክቸር) አንፃር ጎንደር ብዙ መልክ የሚታይባት ከተማ ነች፡፡ ‹‹የሣር ክዳን ባላቸው የጎጆ ቤቶች መሐል፤ የአውሮፓውያንን የቤት አሰራር ወግ የተከተሉና በኢየሱሳውያን ወይም በፖርቹጋል ዜጎች የተገነቡ ቤቶች አዛም - እዚህም ይታያሉ›› የሚለው ፖንሴት፤ ‹‹ከሥነ ውበት አንፃር፤ ጎንደር እንደኛ ከተሞች ያለ ውበት የላትም፡፡ ሊኖራትም አይችልም›› ሲል ይደመድማል፡፡

የሆነ ሆኖ፤ጎንደር ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር የጋራ የሆነ ልዩ ገፅታ እንዳላት እና ከ1668 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ጀምሮ የመዲናዋ የጎንደር ነዋሪዎች ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የመኖሪያ ሰፈር ከፍፍል እንደነበራት ይጠቅሳል፡፡ ሪቻርድ ፓንክረስት እንደሚሉት፤ በ1699 ዓ.ም (እኤአ) ከጎንደር ነዋሪዎች ግማሽ ገደማ የሚሆኑት፤ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ተከታዮች፤ አንድ አራተኛው ሙሰሊሞች፤ አንድ አራተኛዎቹ ደግሞ ፈላሾች ሲሆኑ፤ በቁጥር ጥቂት የሆኑ ካቶሊኮችም ይኖሩ ነበር፡፡ እንደ ፖንሴት ገለፃ፤ ‹‹እነኝህ ካቶሊኮች በአብዛኛው ከፖርቹጋል አባት የተወለዱ ሀበሻ ዲቃሎች ወይም ከኢየሱሳውያን ሚሽን የካቶሊክ እምነትን የተቀበሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሆኖም እምነታቸውን የሚያከናውኑት በስውር ነበር፡፡››

‹‹በአዋጅ እንደ ተደነገገው›› ይላል ቻርልስ ፖንሴት፤ ‹‹ሙስሊሞች፣ ካቶሊኮች እና ፈላሻዎች (ኢትዮጵያዊ አይሁዶች ወይም ጥቁር አይሁዶች) ከኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ አይፈቀድም፡፡ ይህ ህግ በተለይ በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ጠንከር ይል ነበር፡፡ ክርስትያን ኢትዮጵያውያን እስላሞችን ከአውሮፓውያን እኩል ይርቋቸው ነበር›› ይላል፡፡

እንደ ዶ/ር ፖንሴት አስተያየት፤ ይህ ጥላቻ የተፈጠረው በ13ተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ፤የአካባቢው እስላሞች ሐገሪቱን ለመውረር ሙከራ ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ ‹‹ይሁንና›› ይላል ፖንሴት አያይዞ፤‹‹በጎንደር የእስላሞችን መኖር መቀበል ባይቸግራቸውም፤ አውሮፓውያን ካቶሊኮችን ግን ፈፅሞ ማየት አይፈልጉም›› ይላል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሐገሪቱ ኢኮኖሚ (ንግድ) ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው የሚገልፀው ዶ/ር ቻርልስ ፖንሴት፤‹‹በኢትዮጵያ ንግድ በአብዛኛው በሙስሊሞች እጅ ነው፡፡ አብዛኛው የንግድ መስመር የተዘረጋውም ሙስሊሞች በሚኖሩባቸው ግዛቶች ነበር፡፡ ክርስቲያኖቹ የፖለቲካ ሥልጣኑን ሙሉ ለሙሉ እንደያዙት ሁሉ፤ የሐገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ወይም የንግድ ሐብት በሙስሊሞች እጅ የተያዘ ነው፡፡ ይህም ሆኖ፤ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጋር ተቀላቅለው እንዳይኖሩ በህግ ክልከላ ተጥሎባቸዋል፡፡ ስለዚህ የራሳቸውን መንደር ለይተው በየከተማው ዳርቻ አካባቢ በሚገኙ የተለያዩ መንደሮች ሰፍረው ይኖራሉ›› ይላል፡፡

በአጠቃላይ ስለኢትዮጵያ ህዝብ አደረጃጀት ሲገልፅ፤ጥንታዊ የዘር ሐረግን መሠረት ያደረገ የፊውዳል ማህበረሰባዊ መዋቅር እንዳለና በማህበረሰቡ ውስጥ የመጨረሻውሥልጣን የንጉሡ እንደሆነ የሚያወሳው ፖንሴት፤ ሐገሪቱም ጥብቅ ትስስር በሌላቸው ጠቅላይ ግዛቶች የተከፋፈለች መሆኗን ይናገራል፡፡ ‹‹ስለዚህ በየጠቅላይ ግዛቱ ያለውን ህዝብ አንድ ያደረገው ነገር፤ህዝቡ ለኦርቶዶክስ ሐይማኖት ያለው ጥልቅ እምነት እና ለውጭ ሰዎች [አውሮፓውያን] ያለው ጥላቻ ነው›› ሲል ፅፏል፡፡

እንደ ትግራይ ያሉ አንዳንዶቹ ጠቅላይ ግዛቶች፤ ሰፊ ግዛት እንዳላቸው የሚገልፀው ዶ/ር ቻርለስ ፖንሴት፤ የትግራይን የቆዳ ስፋት ከሐገሩ ፈረንሳይ ጋር ያነፃጽረዋል፡፡ ሌላው የሚያነሳው ጠቅላይ ግዛት ጎጃም ሲሆን፤ በዚህ ጠቅላይ ግዛት በርካታ የወርቅ ማምረቻ ጉድጓዶች እንዳሉ ይገልፃል፡፡

ቻርልስ ፖንሴት፤ ሠራዊቱ እና የቤተመንግስቱ አስተዳደር ከዚህ የወርቅ ምርት በሚገኘው ገንዘብ እንደሚደገፍ እና በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ያለው የሠራዊት ብዛት አምስት መቶ ሺህ እንደሚደርስ ግምቱን አስፍሯል፡፡ ‹‹የሐገሪቱ ሐብት እና ስልጣን ሙሉ በሙሉ የንጉሠ ነገስቱ ነው፡፡ ንጉሡ የፈለገውን ይሰጣል፤ የፈለገውን ይነሳል፡፡ አንድ መስፍን በሞተ ጊዜ ንጉሡ የሟቹን መስፍን መሬት እና ንብረት መጠየቅ ይችላል፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለት - ሦስተኛው መሬት ወይም ግዛት ለህጋዊ ወራሾቹ ተመልሶ ይሰጣል፡፡ ቀሪው ሐብት እና ግዛት ግን እርሱ ለመረጠው ሌላ መስፍን ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህ ጉልት የተሰጠው ሹመኛም በጠቅላይ ግዛቱ የንጉሡ ወኪል ይሆናል፡፡ የየጠቅላይ ግዛቱ ነገስታት እና ሌሎች ሹመኞች፤ እንደ ግዛቱ መጠን ለንጉሰ ነገስቱ ወታደር የማዋጣት ግዴታ አለባቸው፡፡ በዚህ መልክ፣ ጦርነት ሲከሰት፤ ንጉሠ ነገስቱ በአጭር ጊዜ ሰፊ ወታደራዊ ኃይል ለማንቀሳቀስ ይችላል›› ሲል ፅፏል፡፡

ፖንሴት ስለህዝቡ ያን ያህል በቂ መረጃ ለማጠናቀር አልቻለም፡፡ በህዝቡ ዘንድ ለካቶሊክ አውሮፓውያን ከፍተኛ ጥላቻ በመኖሩ እንቅስቃሴው በቤተ መንግስት የተወሰነ ነበር፡፡ ስለዚህ በየጠቅላይ ግዛቱ ያለውን የመንግስት መዋቅር ወይም የመሬት ባላባቱን አስተዳደር በደንብ ለማተት የቻለ አይመስልም፡፡ ከህዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረግ ባለመቻሉም፤ ገበሬው ማንም ሊነቅለው እና ሊተክለው የማይችለው ‹‹እርስት›› እንዳለው ለማወቅ አልቻለም፡፡ ንጉሠ ነገስቱ፤ ለበታች ሹመኞቹ የጉልት መብት መስጠት ቢችልም ‹‹በእርስት›› ላይ ስልጣን የለውም፡፡ ሆኖም የኦርቶዶክስ ቤተክርሰቲያን በኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን እንዳላት እና ሰፊ የመሬት ይዞታም እንዳላት ተረድቷል፡፡

‹‹በሐይማኖታዊ መዋቅሩ ውስጥ ዋናው ባለሥልጣን አቡኑ ሲሆኑ በሥራቸው በርካታ ቀሳውስት፣ ደበተራዎች፣ ዲያቆናት፣ መነኮሳት፣ እና መነኩሲቶች ይተዳደራሉ፡፡ ከመንግስታዊ መዋቅሩም ጋር ጥብቅ ትስስር አላቸው፡፡ አቡኑ ከ4ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከግብፅ የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ገዳማት ተመርጦ የሚሾም ነው፡፡ አቡኑ በሐገሬው ቀሳውስት ላይ ፍፁም ስልጣን አላቸው፡፡ አንዳንዴም ንጉሱን የመገዳደር ኃይል ያሳያሉ፡፡ ፓትሪያርኩ አበምኔቶችን እና አዳዲስ ቀሳውስትን ይሾማል፡፡ አልፎ አልፎ፤ በአንድ ጊዜ ብቻ እስከ 10 ሺህ ካህናትን ይሾማል›› ሲል ፅፏል ፖንሴት፡፡ ‹‹በጠቅላላ ሐገሪቱ የሚኖሩት ካህናት ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ይህን መነሻ በማድረግ መገመት ይቻላል›› ብሏል፡፡

እንደ ፖንሴት ትረካ፤ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በአቡኑ እጅ በመሆኑ፤ በሞት ሲለይ ወይም ባልተገባ ባህርይ ከኃላፊነቱ ሲነሳ ሳይውል ሳያድር በሌላ መተካት ይኖርበታል፡፡ አልፎ አልፎ፤ሐገሪቱ ከእስክንድርያ ጋር ያላት ግነኙነት ቢበላሽ እንኳን፤ በፍጥነት አቡን እንዲላክላት ጥያቄ ከማቅረብ ወደኋላ አትልም፡፡ በአቡኑ ሥር ያሉት ቀሳውስት በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ አላቸው፡፡ እነኝህ ቀሳውስት፤ በቢጫ ልብሳቸው እና በሰማያዊ ቆባቸው ከሌላው ህዝብ ተለይተው ይታወቃሉ፡፡

‹‹ልክ እንደ ካቶሊክ ቄሶች፤የኦርቶዶክስ ካህናት ሐይማኖታዊ ክንውኖችን ይመራሉ፡፡ ሥጋወደሙን ይሰጣሉ፡፡ ለምሣሌ፣አንድ ሰው ንስሀ ሲቀበል፤ ቄሱ በወንበር ላይ ቁጭ ሲል ተነሳሂው ከፊለፊቱ ይንበረከካል፡፡ ከዚያም የሰራውን ሐጢያት ይናገራል፡፡ ነገር ግን፤ ንስሀው [ጥቅል እንጂ ዝርዝር?] አይደለም፡፡ ንስሀውን ሲጨርስም ከሀጢያቱ ይነፃል፡፡ ቄሱ መጀመሪያ ዓይኑን፤ ከዚያም ጆሮውን፣ አፍንጫውን፣ አፉን እና እጁን ይባርካል፡፡ በዚህ ጊዜ ከወንጌል የተለያዩ ክፍሎች ይነበባል›› የሚለው ዶ/ር ፖንሴት፤ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በመሆኑ የንስሀ አተገባበር ስርአቱን ‹‹ጉድለት ያለበት ነው›› ሲል የሰጠውን አስተያየት ለመቀበል ያስቸግራል፡፡

ሆኖም፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ለእምነቱ ባለው ፅናትና ጥልቀት ፖንሴት መገረሙን አልደበቀም፡፡ ለምሳሌ፤ በአንድ ቦታ፤‹‹የኢትዮጵያ ምዕመናን ለቤተክርስቲያናቸው ያላቸው ክብር ትልቅ በመሆኑ፤ ወደ ቤተክርስትያን ሲገቡ ጫማቸውን አውልቀው ነው፡፡ ሲያስቀድሱም፤ ንፁህ የናይለን ልብስ ለብሰው ሲሆን፤ በአውሮፓውያን ዘንድ ባልተለመደ ሁኔታ በቅዳሴ ጊዜ በፍፁም ፀጥታ ስርአቱን ይከታተላሉ›› ብሏል፡፡

‹‹የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በአምልኮ ጊዜ ምንም አይነት ምስል አይጠቀሙም፤ ከምስለ ስቅለቱ በስተቀር፡፡ ይሁንና በሥርአተ ቅዳሴው ጊዜ ያለማቋረጥ እጣን ያጨሳሉ፡፡ በጣም ለጆሮ ተስማሚ በሆነ ዝማሬና የምስጋና መሳሪያዎች ይዘምራሉ›› የሚለው ፖንሴት፤‹‹ካቶሊኮች እና የኮፕቲክ ክርስቲያኖች በቅዳሴ ጊዜ የሚያነቡት የወንጌል ቃል ተመሳሳይ ነው፡፡ ተመሳሳይ ቅዱሳንን ያከብራሉ›› ይላል፡፡

ዶ/ር ፖንሴት፤ የክርስቶስን ስቅለት እና የሌሎች ቅዱሳንን ምስል የሚያሳዩ አነስተኛ ስዕሎችን ለአፄ ኢያሱ በስጦታ አበርክቶ ነበር፡፡ እናም፤ ‹‹ንጉሡ የቅዱሳንን ምስል ተቀብሎ በታላቅ አክብሮት ከሳማቸው በኋላ ወደ ውስጥ እንዲያስገቡለት አዘዘ›› ይላል፡፡

‹‹የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀሳውስት፤ አንድ ወንድ ብዙ ሴት ማግባቱን በጥብቅ ይኮንናሉ፡፡ ሆኖም ንጉሱን ጨምሮ መሳፍንቱ ከአንድ በላይ ሚስት ሲያገቡ ይታያሉ›› ሲል የሚተቸው ፖንሴት፤‹‹በካቶሊክ እና በኦርቶዶክስ እምነት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የኢትዮጵያ ክርስትና፤ከኦሪት ትውፊት ጋር ጥብቅ ተዛምዶ ያለው እምነት ነው›› ይላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፤ ዝርዝር ሐይማኖታዊ ጉዳዮችን የሚያነሳው ፖንሴት፤ ከውጭ ላለ ሰው በግልፅ የሚታይ ጉዳይ ባይሆንም፤ በሐገሪቱ በክርስትና አስተምህሮ ላይ የተመሰረተ ውዝግብ መኖሩን ይገልፃል፡፡ ሆኖም፤ የልዩነቱን መሰረተ ሐሳብ ሊረዳው አልቻለም፡፡ ሐይማኖታዊ ውዝግቡ ለብዙ ዓመታት የዘለቀ እንደሆነ እና ሐይማኖታዊ ክፍፍሉም በገጠር የሚኖረውን ሰፊ ህዝብ እና ቤተመንግስት ያሉ ሰዎችን ጭምር የከፋፈለ ችግር መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ችግሩ፤ ንጉሱን እንኳን በኑፋቄ እንዲጠረጠር ከማድረግ የደረሰ እንደነበርም ያመለክታል፡፡

ዶ/ር ፖንሴት ከንጉሱ ጋር ለብቻ ሆነው ሲወያዩ፤ የኢየሱስን ባህርይ በተመለከተ የግል አስተያየቱን ለማወቅ ጥያቄ እንዳቀረበለትም አስፍሯል፡፡ እንዲሁም ዶ/ር ፖንሴትን በጊዜው ወደነበሩት አቡን እንደላከው እና አቡኑም በአክብሮት እንደተቀበሉት ጠቅሷል፡፡ ታዲያ ንጉሱ ይህን ያደረገው፤ አውሮፓዊ ከሆነ ካቶሊክ ጋር ለብቻ በመነጋገሩ ሊከተል የሚችለውን ጥርጣሬ እና ተቃውሞ ለማስወገድ ነበር፡፡

ቤተክህነት ከፍተኛ ኃይል እንዳላት እና ይህ ኃይል ወደ ተቃውሞ ከተቀየረ ለመንግስቱ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል የጠቀሰው ዶ/ር ፖንሴት፤ አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሳይገናኝ ለብቻው እንዲቆይ እንደ ተደረገም ፅፏል፡፡ ‹‹ላይ ላዩን ሲታይ የንጉሱ ስልጣን ጠንካራ እና ከአደጋ የራቀ ቢመስልም፤ ስልጣኑን የሚገዳደር ብዙ ፈተና ተደቅኖበታል፡፡ ስለሆነም ስልጠኑ እንዲፀና በጥንቃቄ መራመድ ይኖርበታል›› ሲል ፅፏል፡፡

ንጉሱ በግለሰብ ደረጃ የሚከበር ሰው ቢሆንም፤ በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ውስጥ እየተባባሰ የመጣው ክፍፍል ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ብዙ ትግል ማድረግ ነበረበት፡፡ በየአካባቢው ያሉት መሳፍንትም ለስርወ መንግስቱ ያላቸው ከበሬታ ዝቅተኛ መሆኑን አስፍሯል፡፡ ‹‹የንጉሱ ባለሟሎች እንኳን ብዙ የሚታመኑ አይደሉም›› ይላል፡፡

ንጉሱ ለፖንሴት ታላቅ ድምቀት ያለው አቀባበል ማድረጉ፤ በወቅቱ የነበሩትን ፖለቲካዊ እና ሐይማኖታዊ ችግሮች ለመቋቋም ከውጭ መንግስታት ግንኙነት መመስረቱ ያዋጣል የሚል አመለካከት መኖሩን የሚጠቁም ነው፡፡ ስለዚህ ከምዕራብ ኃያል መንግስት ፈረንሳይ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት የመመስረት ዕድል ሲመጣለት አጓጊ ጉዳይ መሆኑ አይቀርም፡፡

አፄ ኢያሱ አጋጣሚውን በመጠቀም፤ ፈረንሳይ የቴክኒክ ዕርዳታ እንድትሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ አርክቴክቶች፣ ግንበኞች፣ አናጢዎች፣ ኢንጅነሮች እና የጦር መሣሪያ የመስራት ጥበብ ያላቸው ባለሙያዎች እንደሚፈልግም ለፖንሴት ገልፆ ነበር፡፡

ዶ/ር ፖንሴት ጎንደር ውስጥ ለዘጠኝ ወራት ተቀመጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ፖንሴት ንጉሱን በደንብ ለማስተዋል ዕድል አግኝቷል፡፡ ንጉሱም ፖንሴትን በልዩ አክብሮት እና ቤተሰባዊ ስሜት ሲያስተናግዱት እንደቆዩ ራሱ ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ የአርባ አንድ ዓመት ዕድሜ ያለው አፄ ኢያሱ፤ የሚደነቅ ልዩ ባህርያት እንዳለው የሚገልፀው ፖንሴት፤ ‹‹ከእነዚህ መካከል፤ ፈጣን እና የሰላ የንግግር ችሎታ [የሰላ አስተውሎት]፣ ለዛና ወግ ያለው ቀልድ አዋቂነት እና የጀግና ተክለ ሰውነት›› የታደለ ንጉስ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ ንጉሱ፤በአብዛኛው በጥብቅ የቤተመንግስት ወግ እና ስርዓት የተከበበ ቢሆንም፤ በዚህ ጉዳይ ሳይታሰር  በጣም ዘና ያለ ባህርይ ይዞ ሥራውን እንደሚያከናውን ዘግቧል፡፡ ይሁን እንጂ፤ በመንግስታዊ ሥራው እና ግብር በሚያበላበት ወቅት፤ የንጉስነት ክብሩን ሳያጓድል እና የነገስታት ወግን በጥንቃቄ ተከትሎ ይንቀሳቀሳል ብሏል፡፡

ፖንሴት ለዚህ እንደ ምሣሌ የሚያነሳው አንድ ነገር አለ፡፡ ኦገስት 10፣ 1699 ዓ.ም ከአፄ ኢያሱ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኝ የነበረው ሁኔታ ከፍተኛ ስርዓትን የተከተለ አቀባበል እንደነበረ ጠቅሷል፡፡ በተለመደው ስርዓት ከንጉሱ ጋር የሚገናኝ ሰው፤ ከዙፋን ቀርቦ እጅ መንሳት እና የንጉሱን እግር መሳም የሚጠበቅበት ቢሆንም፤ እርሱ ይህ ግዴታ እንደተነሳለት ይገልፃል፡፡ የድንግል ማርያም በዐል በተከበረ ዕለት እና ከህዝብ ፊት በሚቀርብ ጊዜ የነበረው ሰልፍ እና ወግ በጣም ልዩ እንደነበርም ያነሳል፡፡ ንጉሱ ለዘመቻ ሲነሳ የሚከናወነው ስርዓት በጣም የተለየ ክብር የሚታይበት እና የእርሱን ታላቅነት ወይም ክብር እንዲሁም ወታደራዊ ግርማ ሞገሱን የሚያጎላ እንደነበረም ፖንሴት ጠቅሷል፡፡ የንጉሱን ክብር ከፍ አድርጎ ለማሳየት ከሚያደርገው ጥንቃቄ በተጨማሪ፤ ለፍትህ መረጋገጥ የሚሰጠው ትኩረትም ልዩ እንደሆነ ፖንሴት ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ ዜና መዋዕሎች በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት ነገር፤ አፄ ኢያሱ በህይወት ዘመኑ ያልተለመደ ደግነት የሚያሳይ ንጉስ መሆኑንና በዚህም ‹‹የተለየ ርህራሔ ያለው ንጉስ›› የሚል ዝና እንዳተረፈ የሚያወሳው ፖንሴት፤ ከዚህ በተጨማሪ በጀግንነት፣ በወታደራዊ ጥበብ፣ በየጊዜው በቤተመንግስት አካባቢ የሚነሳ ሴራን በማክሸፍ ረገድ ያለው ክህሎት የተለየ መሆኑን ያነሳል፡፡

እንደ ፖንሴት ገለጻ፤ አፄ ኢያሱ ንጉሳዊ ህግን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ውጤታማ እንደሆነ እና እንደ ሰው መግደል ያለ የወንጀል ድርጊት የሚሰማው በጣም አልፎ አልፎ መሆኑን ያነሳል፡፡ እንዲህ ያሉ ወንጀሎች ተፈፅመው ሲገኙም፤ ንጉሱ ፍርድ ሲያሳልፍ ርህራሔ አይርቀውም፡፡ የሞት ፍርድ የሚያሳልፈውም፤ የተፈፀመው ወንጀል እንደዚያ ዓይነት ፍርድ የሚጠይቅ ሲሆን ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ በፖንሴት እምነት፤ ‹‹ህዝቡ የዋህ እና ከወንጀል የራቀ ህዝብ የሆነው፤ ጨዋ እና ሐቀኛ ህዝባዊ ባህርይ የተፈጠረው፤ ከሐይማኖት በተጨማሪ በዚህች ሐገር በሰፈነው ትክክለኛ ፍትህ እና እንዲፀና በተደረገው ታላቅ ስርዓት የተነሳ ነው፡፡›› ከሁሉም በላይ፤ ዶ/ር ፖንሴትን በእጅግ ያስገረመው ነገር፤ ንጉሡ ‹‹ወጣ ያሉ የጥበብ እና የሳይንስ ጉዳዮችን›› ለመረዳት ያለው ልዩ ብቃት ነበር፡፡ በተለይም የምዕራቡ ዓለም የህክምና ዘዴን ለመረዳት ያለው ብቃት የሚደነቅ እንደሆነ የሚጠቅሰው ፖንሴት፤ ወደ ኢትዮጵያ ይዟቸው የመጣውን መድሐኒቶች ኬሚካላዊ ባህርይ ለመረዳት አፄ ኢያሱ በሚያሳየው ጉጉት ተደንቋል፡፡

‹‹አፄ ኢያሱ፤ የመድሓኒት ቅመማውን እንዳሳየው ይፈልጋል፡፡ መድሐኒቶቹ የሚያስከትሉትንም ውጤት ለማወቅ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ በዚህ ሳይወሰን ወደፊት መድሐኒቶቹን ለመሥራት እንዲቻል የአሰራር ሂደቱን በሰነድ እንድመዘግብለት ይጠይቀኝ ነበር፡፡ በእርግጥ፤ አፄ ኢያሱ፤ ስለማናቸውም ነገር በምሰጠው ቁሳዊ እና ተፈጥሮአዊ ትንታኔ በእጅጉ ይደሰት ነበር›› ሲል ፅፏል፡፡

አፄ ኢያሱ እና ዶ/ር ፖንሴት፤  በጣና ሐይቅ በሚገኝ የንጉስ ማረፊያ ለመዝናናት ሄደው ለሦስት ቀናት በቆዩ ጊዜ፤ ይኸው ትምህርት መቀጠሉን ጠቅሷል፡፡ በዚህ ጊዜ፤ ንጉሱ እጅግ የተደሰተበትን የኬሚስትሪ ሙከራም ያሳየው እንደ ነበር ጠቅሶ፤ ‹‹የህክምና ጥበብ፤ ከአምልኮ እና ከአስማት ጋር የተያያዘ በሆነበት ምድር፤ የንጉሱ የአስተሳሰብ ብስለት (intellectual sophistication) እና የምዕራባውያንን ሳይንስ ለማወቅ ያሳያው ጉጉት ለፈረንሳዩ የህክምና ሰው አስገራሚ ሳይሆንበት አልቀረም›› ሲል ፅፏል፤ በፖንሴት የጎንደር ጉዞ ላይ ጥናት ያደረገው፤ ‹‹A French Physician at the Court of Gondar: Poncet’s Ethiopia in the 1690s›› በሚል ርዕስ ጥናት ያቀረበው ሮናልድ ኤስ. ላቭ (Ronald S. Love)፡፡

በመጨረሻም፤ እኤአ 1700 ዓ.ም የጸደይ ወራት ፖንሴት ወደ ፈረንሳይ ለመሄድ ልቡ ተነሳሳ፡፡ ከዘጠኝ ወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የለከፈው ህመም ጨርሶ እንዳልተሻለው ለንጉሱ በመንገር፤ ወደ ሐገሩ ለመመለስ እንደሚፈልግ ተናገረ፡፡ ጤንነቱ እየተዳከመ መሆኑን ገልፆ ለመሄድ ጥያቄ ሲያቀርብ፤ ንጉሱ ከፍተኛ ሽልማት እንደሚሰጡት በመግለፅ እንዲቆይ ለማድረግ ሙከራ አድርጎ፤ ሳይሳካለት ቀረ፡፡ እናም ንጉሱ የወርቅ አምባር እና የክብር ካባ ሸልሞ አሰናበተው፡፡

አፄ ኢያሱ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ የሚያለግል አንድ ሰው ከዶ/ር ፖንሴት ጋር እንዲሄድ አደርጎ ነበር፡፡ አምባሳደር ሆኖ የተሾመው ሰው፤ ለሊዊስ 14ኛ የሚበረከት ስጦታ ተሰጠው፡፡ ስጦታውም፤ ፈረሶች፣ አንድ ጥንታዊ መስቀል፣ ፕሮስሊን፣ በልዩ ጥንቃቄ እና ጥበብ የተሰሩ ቁሳቁሶች እና በመንገድ የሞቱ ዝሆኖች ነበሩ፡፡ ከዚህ ሌላ፤ ከአፄ ኢያሱ የተላከ እና በሰም የታሸገ ደብዳቤም ይዞ ነበር፡፡ ‹‹አፄ ኢያሱ ከፈረንሳይ መንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመመስረት ፍላጎት እንዳለው ቢገልፅም፤ የንጉሱ ደብዳቤ በአብዛኛው ሐይማኖታዊ ይዘት የነበረው ነው›› ይላል፤ ሮናልድ ኤስ. ላቭ፡፡

የሆነ ሆኖ፤ ዶ/ር ቻርልስ ፖንሴት እኤአ በ2 ሜይ 1700 ዓ.ም ከጎንደር ወጣ፡፡ ኢትዮጵያን እና ንጉሱን ትቶ መሄድ ጭንቅ ሆኖበት እንደ ነበር፤ ራሱ ከፃፈው ቃል መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹አንድ ሺህ ደግነት ያደረገልኝን አፄ ኢያሱን እንዲሁ እንደ ቀላል ነገር ትቶ መሄድ አልሆነልኝም›› የሚለው ፖንሴት፤ እንዲህ ሲል ሐሳቡን ይቀጥላል፤

‹‹ንጉሱ ራሱ በመለያየታችን ስሜቱ የተነካ ይመስላል፡፡ ይህን ታላቅ ንጉስ ባስታወስኩ ቁጥር፤ ያደረገልኝን ውለታ በታላቅ ስሜት መዘከሬ የማይቀር ነው፡፡ ጤንነቴ ባይታወክብኝ ኖሮ፤ ቀሪውን ዘመኔን ለዚህ ሰው እና መንግስቱን ለማገልገል ለማዋል ወደ ኋላ ባላልኩ ነበር፡፡››

የመልስ ጉዞው፤ በመጣበት የሱዳን በርሃ አልነበረም፡፡ በዚያ መሄዱን ትቶ ወደ ምፅዋ በመሄድ በመርከብ ተሳፍሮ ቀይ ባህርን በመቅዘፍ ወደ ሳዑዲ ጂዳ ሄደ፡፡ ከዚያም ወደ ካይሮ አቀና፡፡ ሰኔ 10 1700 ዓ.ም (እኤአ) ግብፅ ካይሮ እንደደረሰ፤ በካይሮ የፈረንሳይ ቆንስል የሆነው እና ተልዕኮ ሰጥቶ ወደ ኢትዮጵያ የላከው ቢኖይት ዲ ሜይለት (Benoît de Maillet)፤ ትንሽ ይረፍ እንኳን ሳይል፤ስለ ጉዞው መግለጫ እንዲሰጠው ጥያቄ አቀረበለት፡፡ ፖንሴት የሰጠው ምላሽም፤ ‹‹ንጉሱ አምባሳደር ቢልክም፤ ኢትዮጵያውያን ለአውሮፓውያን ያላቸው ጥላቻ ከፍተኛ በመሆኑ፤ የፈረንሳይን ልዑክ በጎንደር ለመቀበል ይቸገራል›› የሚል ነበር፡፡  ሆኖም Benoît de Maillet ይህን ሐሳብ አልተቀበለም፡፡ የእርሱ እምነት፤ የፈረንሳይ መንግስት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን የሚነካ ሥራ እስካልሰራ ድረስ፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመስረት ይቻላል የሚል ነበር፡፡ ስለዚህ፤Benoît de Maillet፤ ለሁለቱ ክርስትያናዊ ነገስታት ጥቅም የሚያስገኝ ግንኙነት መመስረት ይቻላል የሚል ተስፋ ነበረው፡፡ ይህን እየተነጋገሩ ሳለ፤ በዶ/ር ፖንሴት፣ በቆንስሉ Benoît de Maillet እና በኢትዮጵያው አምባሳደር መካከል የጋለ ክርክር ተነሣ፡፡ ክርክሩ የተነሳውም፤ በአፄ ኢያሱ ደብዳቤ ሐሳብ እና በተለይም የአፄ ኢያሱን ደብዳቤ ለሊዊስ 14ኛ የምሰጠው ‹‹እኔ ነኝ - እኔ ነኝ›› በሚል ነበር፡፡  በመጨረሻም የተደረሰበት ስምምነት፤ የአፄውን ደብዳቤ ወደ ፈረንሳይ የሚወስደው ፖንሴት ሆኖ፤ በግብፅ የኢየሱሳውያን ሚሽን የበላይ እና በካይሮ የፈረንሳይ ቻንሰሪ መሪ እንዲያጅቡት ይሁን የሚል ነበር፡፡ የአጼ ኢያሱ መልዕክተኛ ግን፤ሊዊስ 14ኛ መልዕክተኛውን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ በግብፅ እንዲቆይ ተደረገ፡፡ በዓመቱ በመጨረሻ ፖንሴት ፓሪስ ሲገባ፤ የጋለ ፍላጎት እና ስሜት የተንፀባረቀበት አቀባበል ተደረገለት፡፡

ሆኖም፤ ወዲያው በአጼ ኢያሱ ደብዳቤ እውነተኛነት እና ፖንሴት ስለኢትዮጵያ በሰጠው መግለጫ ትክክለኛነት ላይ የጥርጣሬ ሐሳብ ተቀሰቀሰ፡፡ ይህ ጥርጣሬ የተፈጠረውም፤ በ Benoît de Maillet  እና በዶ/ር ቻርልስ ፖንሴት መካከል በተነሳው ክርክር ቅሬታ የገባው Benoît de Maillet ትችት ስላቀረበ ነው፡፡ ሆኖም በስተመጨረሻ፤ የደብዳቤው ትክክለኛነት ተቀባይነት አገኘ፡፡ እንዲሁም፤ በጎንደር ኤምባሲ የመክፈት ጉዳይም ላይ ውይይት ተደረገ፡፡ ግን ከዚያ ውይይት ጠብ ያለ ነገር አልነበረም፡፡ ፖንሴት ከጎንደር ከተመለሰ ከአንድ ዓመት በኋላ በፈረንሳይ እና በስፔን መካከል ጦርነት በመቀስቀሱ የኢትዮጵያ ነገር ጨርሶ ተረሳ፡፡ ‹‹ያም ባይሆን፤ ኢትዮጵያውያን ለአውሮፓ ካቶሊካውያን ያላቸው ጥላቻ ሲታሰብ፤ በጎንደር ኤምባሲ የመክፈቱ ነገር ሊሳካ የሚችል ዕቅድ አይመስልም›› ይላል፤ ሮናልድ ኤስ. ላቭ (Ronald S. Love)፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላም አፄ ኢያሱ ‹‹በእኔ እነግስ›› ውዝግብ ተገደሉ፡፡ ዶ/ር ፖንሴትም በፈረንሳይ የገጠመው ነገር አላስደሰተውም፡፡ ወደ ካይሮ እንዳይመለስም፤ Benoît de Maillet በበቀል ስሜት ስሙን አጥፍቶታል፡፡

ስለዚህ ወደ ህንድ በመሄድ ዕድሉን ለመሞከር ወሰነ፡፡ በቀይ ባህር አድርጎ ወደ ‹‹ሱራት›› ሄደ፡፡ ከዚያም ወደ ፐርሽያ አቅንቶ፤ በ1706 ዓ.ም (እኤአ) የወደቀበት ሳይታወቅ ሞተ፡፡በBenoît de Maillet ጥላቻ የተነሳ፤ የዶ/ር ቻርልስ ፖንሴት ሥራ ጥርጣሬ አጥልቶበት ቢቆይም፤ ወደ ኋላ የመጡ አጥኚዎች፤ በተለይ ለኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ፋይዳ ያለው ሥራ መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡

 

 

 

 

Published in ህብረተሰብ

 

 

 

ምርጫ ቦርድ የተቃዋሚዎች ውንጀላ መሰረተቢስ ነው ብሏል

ባለፈው እሁድ በተከናወነው 5ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተወዳደሩ ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣የምርጫውን ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ግድፈቶችና የህግ ጥሰቶች መፈጸማቸውን ጠቅሰው የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉ አስታወቁ፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በ442 የምርጫ ክልሎች ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ እንዳሸነፈ መግለጹን ተክትሎ  መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓና መኢአድ የምርጫውን ውጤት አንቀበለውም ብለዋል፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እጩዎች ለውድድር ያቀረበው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፣ምርጫውን አስመልክቶ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው መግለጫ፤ የምርጫውን ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ግድፈቶችና የህግ ጥሰቶች በመፈጸማቸው የምርጫውን ውጤት ሙሉ ለሙሉ እንደማይቀበለው ጠቁሟል፡፡  

በቅስቀሳ ወቅት በአባላትና ደጋፊዎች ላይ ወከባ መፈፀሙንና በምርጫው ዕለት ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያዎች መባረራቸውን የጠቀሰው መድረክ፤ ጉድለቶቹንና ግድፈቶቹን ዘርዝሮ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ማመልከቱንና ምላሹን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ባለፈው ረቡዕ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ 442 የምርጫ ክልሎችን ውጤት ያስታወቀ ሲሆን ኢህአዴግ ሁሉም ላይ ማሸነፉን ጠቁሞ፣ የተቃዋሚዎች ውንጀላ ሙሉ በሙሉ መሰረተ-ቢስ አሉባልታ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡ 

የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤“የዘንድሮ ምርጫ ውጤት ከ2002 ምርጫ የባሰ የሃገሪቱን ዲሞክራሲ ያጨለመ ነው” ብለዋል፡፡ “ባለፈው ምርጫ ቢያንስ ሰረቁ ነው የሚባለው፤ አሁን ግን ዘረፋ ነው ያካሄዱት” ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ኢህአዴጐች በሪከርድነት የያዙትን 99.6 በመቶ ውጤት ወደ መቶ ለማሳደግ አስበው ያደረጉት ይመስለኛል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ኢህአዴግ ያሸነፈው ወደ ዘረፋ ስለገባ ነው እንጂ ተቃዋሚ ስለተዳከመ አይደለም” ያሉት የመድረክ አመራር፤ “ምርጫ በዚህ ሀገር ላይ በትክክል የማይካሄድ ከሆነ በየ5 ዓመቱ ምርጫ እያሉ ህዝብን ከማሰቃየት፣ እንደነ ሰሜን ኮርያ እና ቻይና የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ነው ብሎ ማወጁ ይመረጣል” ብለዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ የምርጫ ውጤቱን ተመልክቶ “ስልጣን ወይም ሞት” የሚለውን አመለካከቱን መፈተሽ እንደሚገባው ጠቁመውም መንገዱ ብዙ ርቀት አያስኬድም ብለዋል፡፡ “ኢህአዴጎች በዚህ አካሄዳቸው ከቀጠሉ ማንንም የማትጠቅም ኢትዮጵያን ትተው እንዳይሄዱ ደግመው ደጋግመው ማሰብ አለባቸው” ሲሉ አሳስበዋል - ዶ/ር መረራ፡፡ “ህዝቡ ሰላማዊና ህጋዊ ትግሉን መቀጠል አለበት” ያሉት የፓርቲው አመራር፤ “ምርጫው ተጭበረበረ ብለን እጃችንን አጣጥፈን አንተኛም፤ ህዝቡ ከኛ ጋር ስለሆነ ትግላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡

በምርጫው ከኢህአዴግ ቀጥሎ የተሻለ ድምፅ ያገኘው ሠማያዊ ፓርቲ ትናንት በሰጠው መግለጫ፤ ምርጫው ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከተካሄዱት ምርጫዎች ጋር እንኳ ሊወዳደር የማይችል እጅግ ኢ-ፍትሃዊ፣ ወገንተኛና ተአማኒነት የሌለው በመሆኑ የምርጫውን ሂደትም ሆነ ውጤት አልቀበለውም ብሏል፡፡

“ነፃነት በሌለባት ኢትዮጵያ ህዝባዊ አስተዳደር መትከል ዘበት ነው” ያለው ፓርቲው፤ “በኃይል በተቀማ ድምፅ የሚመሰረት መንግስትም በህዝብ ተቀባይነት የለውም” ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እስከሚከበሩ ድረስ የነፃነት ትግሉ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም ሰማያዊ  አስታውቋል፡፡

በዘንድሮ ምርጫ የተሳተፈው ምርጫውን ሊያስፈፅሙ የሚችሉ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት እንደሌሉ እያስገነዘበ መሆኑን የጠቆመው ፓርቲው፤በምርጫው ምክንያት የተቃዋሚ ተወዳዳሪዎች፣ ታዛቢዎችና አባላት በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች አፈናና እንግልት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡ “በህገ ወጥ አሰራሮች ታጅቦ የተከናወነ” ሲል የገለጸው የዘንድሮ ምርጫ፤ በምንም መመዘኛ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ሂደት ያልታየበት በመሆኑ ሂደቱንም ውጤቱንም አልቀበለውም ብሏል-ሰማያዊ ፓርቲው፡፡

ከኢህአዴግና መድረክ ቀጥሎ በርካታ እጩዎችን ለምርጫው ያቀረበው የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ በቅድመ ምርጫው ወቅት ኢዴፓ በሚዲያ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች ሳንሱር እየተደረጉበት መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻቸውን አስታውሰው፣በምርጫው ላይ ችግር መታየት የጀመረው በሂደቱ ላይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በሂደቱ ወከባዎች በዝተውብን ነበር ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ በነዚህ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ፓርቲያቸው በሂደቱ መሳተፍ መቀጠሉን ጠቁመው ሂደቱ ከህግ አፈፃፀም አንፃር ዲሞክራሲያዊ ነበር ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

 የኢህአዴግ ፅ/ቤት የህዝብና ኮሚኒኬሽን ኃላፊው አቶ ደስታ ተስፋሁ በሰጡት አስተያየት፤ “ሂደቱ ጥሩ ነው ብለው ወደ ምርጫው ከገቡ በኋላ ውጤት አይቶ ሂደቱ ትክክል አልነበረም ማለት ተቀባይነት የለውም” ሲሉ የኢዴፓን ሃሳብ ተቃውመዋል፡፡   አንዳንድ ፓርቲዎች በሂደቱ አምነው ከገቡ በኋላ ህዝብ እንዳልመረጣቸው ሲያውቁ ምርጫው ተቀባይነት የለውም ማለታቸው እኛ ካላሸነፍን ከሚል አባዜ የሚመነጭ ነው ያሉት  አቶ ደስታ፤ በምርጫው ህዝቡ መብቱን በትክክል ተግባራዊ ስለማድረጉ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች ታዛቢዎች ያረጋገጡት በመሆኑ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ማለት ለህዝቡ ውሳኔ ያለመገዛት ፀረ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ “ፓርቲዎች ህዝብ ለምን አልመረጠኝም ብለው ራሳቸውን መገምገም እንጂ ድክመታቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ማዞር የለባቸውም” ብለዋል አቶ ደስታ፡፡

ከምርጫው በፊት የገዢው ፓርቲ አባላት ህግ በመጣስ ብዙ አፈናዎችና ወከባዎች ሲፈጽሙ ነበር ያሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት፤ በምርጫው እለት የፓርቲያቸው ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያዎች መባረራቸውን ጠቁመው፣“ታዛቢዎች በሌሉበት የተካሄደው ምርጫ ተአማኒ ነው ብለን አናምንም” ብለዋል፡፡ “ምርጫው ሚስጢራዊ በሆነ ሁኔታ አይደለም የተከናወነው” የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “መራጮች እየተገደዱ ሲመርጡ ታዝበናል፣አሁንም ድረስ ታዛቢዎቻችን ለምን የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ሆናችሁ በሚል እየተዋከቡብን ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ቅድመ ምርጫውም ሆነ የምርጫው እለት እንዲሁም ውጤት አገላለፁ የምርጫ ደንቦችንና ህጎችን ሙሉ በሙሉ የጣሰ ነው ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ ምርጫ ቦርድ ከአደረጃጀት አኳያ ራሱን ሊፈትሽ የሚያስገድደው ሂደት ተስተውሏል ብለዋል፡፡ የምርጫ ውጤቱ አገላለፅ ህዝቡ ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኝ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ውጤቱን ሙሉ ለሙሉ ለምን መግለፅ እንዳልተቻለ ጠይቀዋል፡፡

“መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምፅ ለማግኘት አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም የተወሰነ ወንበር በፓርላማ እንደምናገኘን  ጠብቀን ነበር፤ነገር ግን ምርጫው አሳታፊ ባለመሆኑ አልተሳካም” ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው የሚጠብቀው ዓይነት ምርጫ እንዳልተደረገ ጠቁመውም አሳታፊ ባልሆነ ሂደት ሰላማዊ ትግሉን የትም ማድረስ እንደማይቻል ገልፀዋል፡፡

ኢዴፓ ስትራቴጂውን እንደገና በመቀየር ለተሻለ ትግል እንደሚዘጋጅ በመጠቆምም ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ከሚከተሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ግንባር ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ ማቀዱን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ፓርቲው በምክንያታዊነት መንቀሳቀሱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ፓርቲያቸው ከገዢው ፓርቲ ጋር ከፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ባለፈ በተለየ ሁኔታ መነጋገር እንደሚፈልግም ዶ/ር ጫኔ አስታውቀዋል፡፡ ሌላው የምርጫ ተፎካካሪ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ እንዲሁ፤ የምርጫውን ውጤት ለመቀበል እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ “የተሰራው ስራ ለሀገር የሚበጅ አይመስለኝም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “ምርጫው ትክክለኛ አይደለም፤ አንቀበልም” ብለዋል፡፡ በሃገሪቱ ትክክለኛ ዲሞክራሲ ለማምጣት ጥረት የሚያደርጉ አካላትን ተስፋ የሚያስቆርጥ የምርጫ ውጤት መሆኑን የጠቆሙት አቶ አበባው፤ በሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጣት የማይቻል ከሆነ የፓርቲዎች መኖር ጥቅም የለውም ብለዋል፡፡ ምርጫ የህዝብ ፍላጎት በትክክል የማይገለፅበት ከሆነ የትግሉ ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል ሲሉም አቶ አበባው አክለዋል፡፡ የምርጫ ውጤቱን ረቡዕ ማታ መስማታቸውን የተናገሩት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግስቱ አወሉ፤ስለ ምርጫው መረጃዎች እያሰባሰቡ እንደሆነና አቋማቸውን ለመግለጽ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ መወያየት ስላለበት ምላሽ ለመስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፌድሃግ) በበኩሉ፤ህዝብ ለመረጠው አካል እውቅና እንደሚሰጥ ጠቁሞ፣ለቀጣይ ምርጫ  ድክመትና ጥንካሬውን ገምግሞ ዝግጅት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ረቡዕ 442 የምርጫ ክልሎችን ውጤት ይፋ ያደረገ ሲሆን በሁሉም ክልሎች ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና አጋሮቹ ማሸነፋቸውን ገልጧል፡፡

 ምርጫው በታሰበለት የጊዜ ሰሌዳ ያለምንም ችግር አሳታፊ፣ ፉክክር የታየበትና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ተጠናቋል ያሉት የቦርዱ አመራሮች፤ከምርጫው ጋር የተገናኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅሬታዎችን መሰረተቢስ ናቸው በማለት ውድቅ አድርገዋቸዋል፡፡ “በምርጫው እለት ታዛቢዎችን ተባረውብናል፣ ኮሮጆዎች ሳይፈተሹ ድምፅ ተሰጥቷል፣ ኮሮጆዎች ተቀይረዋል፣ ምርጫው ተጭበርብሯል----የሚሉት መሰረተ ቢስ አሉባልታ ነው” ብለዋል - አመራሮቹ፡፡

 

 

 

 

 

 

Published in ዜና

 

 

 

“የዲሞክራቲክ ተቋማት አለመጠናከር በምርጫው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል” የአሜሪካ እምባሲ

 የዘንድሮውን ምርጫ የመታዘብ እድል ያላገኘው የአውሮፓ ህብረት፤ ምርጫው በተለያዩ ተፅዕኖዎች መሃል የተደረገ እንደነበር የገለፀ ሲሆን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ፤ ምርጫው ሰላማዊ ቢሆንም የዲሞክራሲ ተቋማት አለመጠናከር በምርጫው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል ብሏል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ ሃገሪቱ ሰላማዊ የምርጫ ሂደት ማስተናገዷን ጠቅሶ ከምርጫው በፊት የጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች መታሰር መታሰር እንዲሁም የጋዜጦችና መፅሄቶች መዘጋት፤ ፓርቲዎች በፖሊሲያቸው ላይ ሰፊ ክርክር እንዳያደርጉ እንቅፋት በመሆን በአጠቃላይ የምርጫው እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ምርጫ ቦርድ ላሳየው ትጋትና የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ላቀረበው የትዝብት ሪፖርት እውቅና ሰጥቶ፣ በሃገሪቱ የሲቪክ ማህበራት ላይ የተጣለው ገደብ፣ የሚዲያ ነፃነትና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት በሚገባ አለመከበሩ አሳሳቢና በዲሞክራሲያዊ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

“ምርጫውን ለመታዘብ ፈልገን ተከልክለናል” ያለው ኤምባሲው፣ ሌሎች አካላትም ምርጫውን እንዳይታዘቡ መደረጉና የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች ምርጫውን በተገቢው ሁኔታ መታዘብ አለመቻላቸው በምርጫው የታዩ ጉልህ ግድፈቶች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡የአውሮፓ ህብረትም ሆነ የአሜሪካ ኤምባሲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሰረት በማድረግ በአካባቢያዊና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጋር ለወደፊትም በጋራ እንደሚሰሩ በመግለጫቸው አስገንዝበዋል፡፡ የዘንድሮው ምርጫ ብቸኛ አለማቀፍ ታዛቢ ቡድን በመሆን የታዘበው በናሚቢያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሄፊኬቱንዬ ፖሃምባ የተመራው የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድን ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ ምርጫው ተአማኒና ሰላማዊ ነው ቢልም በምርጫው እለት የታዘባቸውን ግድፈቶች በዝርዝር ገልጿል፡፡ ህብረቱ በሃገሪቱ ካሉት 45ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች በ356ቱ ብቻ 59 አባላቱን በማሰማራት መታዘቡን ጠቁሞ ከታዘባቸው ጣቢያዎች መካከል በ22.7 በመቶ በሚሆኑት የምርጫው እለት የቅስቀሳ መልዕክቶችና ፖስተሮች ሲሰራጩ እንደነበር፣ 23 በመቶ በሚሆኑት ደግሞ በምርጫ ጣቢያ ውስጥ ቅስቀሳ ሲካሄድ መታዘቡን ሪፖርት አድርጓል፡፡ ህብረቱ ከተመዘገበው መራጭ በላይ የምርጫ ወረቀት በኮሮጆ ውስጥ የተገኘበት የምርጫ ጣቢያ እንዳጋጠመውና የኮሮጆ ፍተሻ ሳይካሄድ ምርጫ የተጀመረባቸው ጣቢያዎችን እንደታዘበ ጠቁሟል፡፡ ህብረቱ ይፋ ባደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፤ ጉድለቶች ቢኖሩም ምርጫው ሰላማዊ የተረጋጋና ተአማኒ እንደነበር የገለፀ ሲሆን ከሁለት ወር በኋላ ሙሉ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

 

 

 

Published in ዜና

ገንዘቡን ለፍትህና እኩልነት ለሚታገሉ ድርጅቶች እሰጣለሁ ብሏል

 ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ በእስራኤሏ ባት ያም ከተማ በፖሊስ የድብደባ ጥቃት የደረሰበት ኢትዮ-እስራኤላዊው ወታደር ዳማስ ፓካዳ፣ የተፈጸመብኝ ጥቃት ከዘረኝነት የመነጨ ነው ሲል በአገሪቱ ፖሊስ ላይ ክስ መመስረቱንና ለደረሰበት ጉዳት የ100 ሺህ ዶላር ካሳ እንዲሰጠው መጠየቁን “ታይምስ ኦፍ እስራኤል” ዘገበ፡፡የ19 አመት ዕድሜ ያለው ግለሰቡ ባለፈው ማክሰኞ በቴል አቪቭ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአገሪቱ ፖሊስ ላይ በመሰረተው ክስ፣ ለደረሰበት ጉዳትና ጉዳዩን በህግ ለመከታተል ላወጣው ወጪ ካሳ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን፣ ጠበቃውም በግለሰቡ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የአገሪቱ ፖሊስ በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጽመውን ስነምግባር የጎደለውና ሃይል የተቀላቀለበት ጥቃት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ግለሰቡ በፖሊሶች ጥቃት ሲፈጸምበት በካሜራ ባይቀረጽና ለማስረጃነት ባይቀርብ ኖሮ፣ ምናልባትም ፖሊስን በመድፈር ከባድ ወንጀል ተከሶ ሊቀጣ ይችል እንደነበር የገለጸው ክሱ፣ ጥቃቱ በግለሰቡ ላይ አካላዊና መንፈሳዊ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር የመላውን ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላዊ ልብ የሰበረ ነው ብሏል፡፡  ፓካዳ በፍርድቤት ተከራክሮ ካሸነፈና የጠየቀውን የገንዘብ ካሳ የሚያገኝ ከሆነ፣ የተወሰነ ያህሉን ገንዘብ ለፍትህና ለእኩልነት ለሚታገሉ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ድርጅቶች ለመስጠት ማሰቡን ተናግሯል፡፡

ሁለት የፖሊስ ባልደረቦች በግለሰቡ ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ የሚያሳየው አጭር የቪዲዮ ምስል፣ በስፋት መሰራጨቱንና በቴል አቪቭ በሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ መፍጠሩን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁና የፖሊስ ኮሚሽነሩ ዮሃናን ዳኒኖ ግለሰቡን በአካል አግኝተው ለተፈጸመበት ጥቃት በፖሊስ ስም ይቅርታ መጠየቃቸውና ከሁለት ሳምንታት በፊትም ጥቃቱን የፈጸመው አንደኛው ፖሊስ ከስራ መባረሩ ይታወሳል፡፡

 

Published in ዜና

*በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ቅስቀሳ ሲካሄድ መታዘቡን  ጠቁሟል

የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን፤ ባለፈው እሁድ የተካሄደው የኢትዮጵያ አገራዊ  ምርጫ ከአንዳንድ ጥቃቅን ችግሮች በቀር ሰላማዊና ተዓማኒ ነው አለ፡፡  በአንዳንድ የምርጫ ጣቢዎች ለመምረጥ ከተመዘገበው ሰው በላይ ድምጽ የተሰጠባቸው ወረቀቶች መገኘታቸውን የጠቀሰው ታዛቢ ቡድኑ፤ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ  ቅስቀሳ ሲካሄድ መታዘቡን ጠቁሟል፡፡የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን መሪ የቀድሞ የናምቢያ ፕሬዚዳንት ሂፊኬፑንዬ ፖሃምባ  በትላንትናው ዕለት በሂልተን ሆቴል የህብረቱን  የመጀመሪያ ዙር ሪፖርት ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደጠቆሙት፤ ከ23 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ 59 አባላት በገጠርና በከተማ በሚገኙ 356 የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ታዝበዋል፡፡

ህብረቱ በታዘባቸው 95 በመቶ ያህል  የምርጫ ጣቢያዎች፣ የመራጮች ምስጢራዊነት የተጠበቀ መሆኑን  የጠቆመው የቡድኑ ሪፖርት፤ በምርጫ ጣቢያዎች ምንም የጎላ ችግር አልተከሰተም ብሏል፡፡ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጩ ህዝብ ቁጥር ከ1ሺ በላይ እንደነበር የጠቆመው የታዛቢ ቡድኑ፤ ይሄም በአንዳንድ ጣቢያዎች ለታየው  መጨናነቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጾ፣የምርጫ ህጉንም  ይቃረናል ብሏል፡፡

  ህብረቱ ከታዘባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ 22.7 በመቶ በሚሆኑት የቅስቀሳ መልዕክቶችና ፖስተሮች ሲሰራጩ እንደነበር የገለጸው  ሪፖርቱ፤ 23 በመቶ በሚሆኑት ደግሞ በምርጫ ጣቢያ ውስጥ ቅስቀሳ ሲካሄድ መታዘቡን ጠቁሟል፡፡  በምርጫ ጣቢያው የተመዘገበው መራጭ ቁጥርና  ድምጽ የተሰጠባቸው ወረቀቶች አልተጣጣሙም ከተባሉባቸው አካባቢዎች መካከል ህብረቱ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ምርጫ ጣቢያ 10ን ለአብነት ጠቅሷል፡፡ በዚህ ጣቢያ የድምጽ ቆጠራ ሲከናወን፣ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገበው መራጭ ቁጥር በላይ ድምጽ የተሰጠባቸው ወረቀቶች መገኘታቸውን  ህብረቱ ጠቁሟል፡፡ምርጫው የተረጋጋ፣ ሰላማዊና ተዓማኒ  ነው ያለው የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን፤ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ የፈለገውን በድምጹ እንዲወስን ዕድል ሰጥቶታል ሲል ሪፖርቱን አጠቃሏል፡፡  59 ታዛቢዎችን ያሰማራው የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድን፤ በአገሪቱ ካሉት 45ሺ የምርጫ ጣቢያዎች  በ356 ጣቢያዎች ብቻ ተዘዋውሮ መታዘቡን አስታውቋል፡፡

Published in ዜና

 

 

 

ጓደኛዬ ቆርጣለች። ከዚህ ቀደም እንዲህ ቆርጣ ግን አታውቅም፡፡ ድንገት እኮ ነው ከመሬት ተነስታ (ለነገሩ ከመሬት አልተነሳችም፤ ወንበር ላይ ቁጭ ብላ ነው) “አንቀፅ 38 የሰጠኝን መብት እጠቀማለሁ” ያለችኝ። እኔ ደግሞ ሰው ከተንኮልና ከክፋት ሲፀዳ አይቼ በደህና ጊዜ ከእውቀት የፀዳሁ ስለሆንኩ፣ “አንቀፅ 38 ደግሞ ምንድነው?” ስል ጠየቅኋት፡፡

“ህገ - መንግስቱ የሰጠን መብት ነው። አንቀፅ 38 የመምረጥና የመመረጥ መብት!” አለችኝ ፍርጥም ብላ። አሃ! ምርጫ ደርሶ የለ? የምትለው በጥቂቱ የገባኝ መሰለኝ።

“ልትመርጪ አስበሽ ነው? ታዲያ ምን ታካብጃለሽ? ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነቅሎ ወጥቶ እንደሚመርጥ ኢቢሲ በየቀኑ ይናገር የለም እንዴ!” አልኳት ኮስተር ብዬ።

“አንቀፁ የመምረጥ ብቻ ሳይሆን የመመረጥ መብትም ይሰጣል። እኔ መመረጥ ነው የምፈልገው፤ ፓርቲ አደራጅቻለሁ” አለችኝ:: 

እቺ ልጅ ምን ነካት? የቁንጅና ውድድር መሰላት እንዴ? (ብቻ ቁንጅናንም ሙያ አድርጋው ምረጡኝ እንዳትል አልኩ- በሆዴ!)

“ጓደኛዬ፤ ቁንጅናሽ በኢቢሲ ታየም አልታየም የሚያመጣው ለውጥ የለም። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው የሥልጣን አክሊል የሚደፋ እንጂ የውበት አክሊል የምትደፋ ቆንጆ አይደለም። ይልቅስ የፈላጊዎችሽን በር እንዳትዘጊ” ስል አስጠነቀቅኋት፡፡ እሷ ግን ማስጠንቀቂያዬን ከቁምነገር የቆጠረችው አትመስልም፡፡

“በምርጫው አሸንፌ ቀጣዩን አምስት ዓመት ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ።” አለችኝ አይቼባት በማላውቀው ድፍረት፡፡ አሁን እንዳበደች ገባኝ። በቃ አንዱ በውበቷ የነሆለለ ጎረምሳ ያሰራባት “መስተፋቅር” ዶዙ በዝቶ ጭንቅላቷ ላይ ወጥቷል ማለት ነው ብዬ ደመደምኩ፡፡

ጉዷን ልስማ ብዬ ድምፄ እየተርገበገበ፤ “እንደው ምርጫ ለመወዳደር ምን አሳሰበሽ?” ስል ጠየቅኋት።

ጓደኛዬ ተከዘች። ከንፈሯን ነከስ ነከስ እያደረገች ዮጋ እንደሚሰራ ሰው ተመሰጠች፡፡ ቀጣይ የሀገር መሪ ለመሆን ያለመችው ጓደኛዬ፣ ከስልጣኗም ባታካፍለኝ ቀጣዩ የሀገር ውስጥ ኑሮዬ ሰላማዊ እንዲሆን እንክብካቤ በተሞላበት ድምፀት፤ “እባክሽ ንገሪኝ፤ ተጨነቅሁ እኮ” አልኳት።

“ይኽውልሽ ---- ሀገር ለመምራት ያነሳሳኝ ያለፈው ታሪኬ ነው”

ኧረ ወየው ይቺ ልጅ ብሶባታል አልኩ - በሆዴ። የትኛው ታሪኳ ይሆን? እሷ እኮ መስተዋት ፊት ከመቆምና ወንዶች ከመቀያየር ያለፈ ታሪክ የላትም። ብቻ  በውስጤ ፈገግ አልኩ።

“ይኸውልሽ” አለች መጨረሻው ያማረኝ ወሬዋን ለመጀመር እየታሸች። “ሴት ነኝ” (“ወንድ ብትሆኚማ በዚህ ቁንጅናሽ እስከዛሬ እለቅሽ ነበር?” አልኩ ለራሴ) “ሴት ልጅ ደግሞ ክብረ ንፅህና ይኖራታል” (እንደው ምን ከዕውቀት የጸዳሁ ነኝ ብል ይችን ማወቅ ያቅተኛል?!) ግን ለምንድን ነው ሰው ወደ ፖለቲካ ሲገባ ነገር የሚያካብደው? በእርግጥ የቆንጆዋን ጓደኛዬን ወደ ፖለቲካ መግባት ገና አልተቀበልኩትም፡፡

ጓደኛዬ ቀጠለች ማብራሪያዋን፡፡ እኔም ጭንቅላቴን እየነቀነቅሁ ጉዷን ማዳመጥ ቀጠልኩ።

 “ታዲያ የድንግልና አካሄዱን ከውሃና መብራት አካሄድ ጋር አመሳስለው ቢሄድም ይመጣል በሚል ሴት እህቶቼ በከንቱ ውድ ንብረታቸውን እንዲያጠፉ አልፈልግም” አለች። (እቺ ጠጋ ጠጋ ያልወደቀ እቃ ለማንሳት ነው! አሉ) ብቻ የእኔም “ንብረት” አለ እንዳትለኝና ጉድ እንዳይፈላ። የፈለገ በምርጫ  እወዳደራለሁ ብትለኝም ልታገሳት ዝግጁ አልነበርኩም፡፡ (እየተዋወቅንማ አንታለልም!)

“አየሽ ጓድ” አለችኝ እጩዋ ተወዳዳሪ (እየመጣሽ ተኚ… ጭራሽ ጓድ?) ግርም አለችኝ፡፡ በአንድ የትግል ሜዳ የተዋጋን ሁሉ ሳይመስለኝ አልቀረም፡፡

“አየሽ ጓድ፤ የድንግልናዬን አካሄድ ሳስብ በጎ ትዝታ የለኝም፡፡ ጣዕሙንና ምንነቱን ሳላውቀው ነው ድንገት የሄደው፡፡ እንደ ድንገተኛ አደጋ በይው! እናም እኔ ከተመረጥኩ ይሄ ዓይነቱ የድንግልና አካሄድ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ እንዳይደርስ ጠንከር ያለ ህግ አወጣለሁ”

በጓደኛዬ ነገረ ሥራ እየተገረምኩ፤ “ለመሆኑ የምርጫ ምልክትሽ ምንድነው?” አልኳት።

“ቀይ መሃረብ!” አለችኝ ፈጠን ብላ፡፡

“ቀይ እኮ የአደጋ ምልክት ነው!” ከምሬ ነበር።

“ታሪክ የመለወጥ አላማ ነው ያነገብኩት” አለችኝ ኮስተር ብላ፡፡

“ለነገሩ እኔ ምን አገባኝ”

“እኔ ምን አገባኝ ነው ሀገሬን የገደላት”

እቺ ናት ፖለቲከኛ! ገና ከአሁኑ “የኔ” ብላ እኔን ያለ ሀገር ታስቀረኝ?! (ስትመረጥማ ከሀገር ታሰድደኛለች!)

“ድንግልናችን በድንገት መሄዱ ሳያንስ ባል ተብዬው በስሙ ያወጣው ሲም ካርድ ይመስል የት አደረግሽው? ለማን ሰጠሽው ብሎ ያፋጥጠናል፡፡ በዚህ ጊዜ የእኛ ድንግልናችን ተመልሶ ያልመጣልን ሴቶች መከራና ጭንቀት አይጣል ነው፡፡ በዚያ ላይ እኮ ወንዱ ድንግል ይሁን አይሁን ማንም አይጠይቀው፡፡ ጫናው ያለው ሴቷ ላይ ብቻ ነው!”

“ይሄ እኮ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው” አልኳት ጓደኛዬን፡፡ (ማለቴ እጩ ተወዳዳሪዋን!)

“አዎ ተፈጥሮ ነው፤ እኛ እንደ ሀገር መስራት የምንችለው ላይ ነው የምናተኩረው!”

“እሺ” አልኳት ደሞ ምን እንደምትቀጥል መገመት እያቃተኝ። ሰው እንዲህ በአንዴ ይለወጣል? (አይ ፖለቲካ! አይ ስልጣን! አይ ምርጫ! አይ ፓርቲ!)

 “ታዲያ ቅስቀሳውን ምን ላይ አተኩረሽ ልታደርጊ አሰብሽ?” ስል ጠየቅኋት፡፡

“የእኔ ፓርቲ ከተመረጠ ድንግልና ወይም ክብረ ንጽህና አዳኝ ወንዶችን በመከታተልና በመልቀም ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀጣይ አምስት አመት የልጃገረዶች ሽፋንዋ በ30 በመቶ እንዲያድግ የሚሰራ ይሆናል። ድንግል መፈለግ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዳጅ እንደ ማውጣት የሚታይበትን ዘመን በመቀየር፣ ኢትዮጵያ ነዳጅ አምራች አገር ባትሆንም ልጃገረድ አምራች ሀገር በማድረግ፣ በድንግል መሬቷ ብቻ ሳይሆን በድንግል ሴቶቿም ተመራጭ እናደርጋታለን። ቀድሞ የተወሰዱ ድንግልናዎችን ባናስመልስም በቀጣይ ይህ ታሪክ እንዳይደገም በቁርጠኝነት እንሰራለን!”

ለአፍታ ትንፋሽ ከወሰደች በኋላ ማብራሪያውን ቀጠለችበት፡፡ እንደ ከረመ ፖለቲከኛ ፕሮፓጋንዳ ሁሉ ሳትጀምር አልቀረችም፡፡ (ለነገሩ እሷስ ለፕሮፓጋንዳ ምን ይጎድላታል!?)

“በተጨማሪም የወንዶች ለከፋና ትንኮሳን በትጋት እንዋጋለን!” አለች፡፡

 

 

 

 

 

 

ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አላቸው

ለ2,500 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል

የአሐዱ ፒኤልሲ ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት  አቶ ሰለሞን ወንድሜነህ

ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁት በደርግ ጊዜ ነበር። ያኔ ሥራ የሚመድበው መንግሥት ነበር፡፡ እናም በመንግሥት እርሻ ተመድበው በአትክልትና ፍራፍሬ ኮርፖሬሽን ሥራ ጀመሩ፡፡ እዚያ ለ5 ዓመት ከሰሩ በኋላ ለቀው በተለያዩ የግል ድርጅቶች በኃላፊነት ደረጃ በመሥራት ከፍተኛ ልምድ መቅሰማቸውን ይናገራሉ፡፡ በአገር ውስጥ ከሚሰጡ ሥልጠናዎችና በውጭ አገር ከወሰዷቸው አጫጭር ኮርሶች ያገኙት እውቀት ከፍተኛ በራስ መተማመን ፈጠረላቸው፡፡

ይኼኔ የራሴን ቢዝነስ ብጀምር‘ኮ ህይወቴን በተሻለ መንገድ መምራት፣ ለወገኖቼ የሥራ ዕድል መፍጠርና ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ላደርግ እችላለሁ በማለት አሰቡ፡፡ እውቀትና ልምዳቸውን አቀናጅተው በግላቸው ለመሥራት ከተቀጠሩት መ/ቤት ለቀው፣ የዛሬ 23 ዓመት በ10 ሺህ ብር ካፒታል አሐዱ የግል ኩባንያን መሰረቱ፡፡ የአሐዱ ዋና ሥራ ከቡናና ሻይ ልማት ድርጅት ብትን ሻይ ቅጠል እየገዛ መሸጥ ነበር፡፡ ትንሽ ቆይቶም ሻይ ቅጠሉን በፋብሪካ አቀነባብሮና አሽጎ ለገበያ ማቅረብ ጀመረ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ዕቃዎች ከውጭ እያመጡ ማከፋፈል ያዙ፡፡ ሌሎች ትናንሽ ቢዝነሶችንም ይሰሩ ነበር፡፡

ያኔ ቢዝነሱ እንደ ዛሬ ውድድርና ትግል የበዛበት አልነበረም፡፡ “ገና ኢህአዴግ ሥልጣን ይዞ ነጻ ኢኮኖሚ የታወጀበት ጊዜ ስለነበር እንደ እኔ ያሉ ወጣት የቢዝነስ ሰዎች ያለ ብዙ ውጣ ውረድ ጥሩ የመስራት ዕድል ነበረን” ይላሉ፡፡ አሐዱ ሻይ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለተወደደ ገቢያቸው ጨመረ። ሌሎች ቢዝነሶችም አትራፊ ሆነው ካፒታላቸው ሲያድግ፣ የዛሬ 20 ዓመት አሐዱ  ኩባንያ በ500 ሺህ ብር ካፒታል ፒኤልሲ ሆኖ ተቋቋሙ፡፡ብቸኛ የነበረው አሐዱ ዛሬ ወደ ጎን ተንሰራፍቶ 7 እህት ኩባንያዎች አፍርቷል፡፡ መድኃኒት እያስመጣ ያከፋፍላል፣ ዘመናዊ የእርሻ ልማት አለው፣ በሪል እስቴት ተሰማርቷል፣ ፋርማሲዎች አሉት፣ የፓኬጂንግ ፋብሪካና የትሬዲንግ (ንግድ) ድርጅቶች ባለቤት አለው፡፡ እነዚህ ብቻ አይደሉም። ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም ገብቷል። ከእንግሊዙ ቫሳሪ ግሎባል ግሩፕ ጋር በእኩል 50፣ 50 የአክሲዮን ድርሻ በቢሾቱ ከተማ ያቋቋሙትና የዛሬ ሦስት ሳምንት የተመረቀው “አሐዱክስ ፉድ ፕሮዳክትስ ኩባንያ” የቦርድ አባል፣ የአሐዱ ፒኤልሲ ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ናቸው - አቶ ሰለሞን ወንድሜነህ፡፡ ኢንቨስተሩ ለምን ወደማኑፋክቸሪንግ እንደገቡ ሲናገሩ፣ ግማሽ ምዕተ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ኢኮኖሚያቸው ያደገው ኮሪያና ቻይናም ሆኑ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ትላልቅ አገሮች የመጀመሪያ መነሻቸው አግሮ ፕሮሰሲንግ ነው፡፡ እኛም አሁን ያተኮርነው በእርሻ ምርቶች ማቀነባበር ነው፡፡ እሱን ማስፋፋት አለብን፡፡ ከአርሶ አደሩና ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰርና ፕሮሰስድ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማውጣት ነው። ትልቁ ሀሳባችን በአግሮ ፕሮሰሲንጉ በብዛት ከሰራን በኋላ በሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ማተኮር ነው ብለዋል፡፡ አቶ ሰለሞን በ1955 ዓ.ም በአሁኑ አርሲ ዞን በአሰላ ከተማ ተወለዱ፡፡ ያደጉትም ሆነ የመጀመሪያና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት የተማሩት እዚያው ነው፡፡ 12ኛ ክፍል በ1972 ዓ.ም አጠናቀቁ፡፡ በቀጣዩ ዓመት ንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ገብተው፣ በአካውንቲንግ (በሂሳብ አያያዝ) በዲፕሎማ ተመረቁ፡፡ በ1975 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው፣ በ1980 የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማኔጅመንት አገኙ። ወደ እንግሊዝ አቅንተው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (ኤምኤ) ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል፡፡

አሐዱ፣ የመጀመሪያ ማለት ነው፡፡ መስራቾቹ ይህን ስም የተጠቀሙት ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው የጠበቀ ቁርኝነት አሐዱ የመጀመሪያው አንድ አምላክ ለማለት ነው፡፡ አሐዱ መድኃኒቶችን ከአውሮፓ፣ ከመካለኛው ምሥራቅና ከአፍሪካ አገሮች እያስመጣ በተመጣጣኝ ዋጋ ያከፋፍላል፡፡ ለገሀር የሚገኘውን አክሱም ፋርማሲ ከመንግሥት ሁለት ሚሊዮን በማይሞላ ገንዘብ ገዝተው አሁን ቅርጫፎቻቸውን 12 አድርሰዋል፡፡ ቅርንጫፎቹም በሸበሌ፣ ሳሪስ፣ 22 አካባቢ፣ ቦሌ ሚካኤል፣ መገናኛ፣ ገርጂ፣ … የሚገኙ ሲሆን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት ያቀርባሉ ብለዋል አቶ ሰለሞን፡፡

በሪል እስቴት ዘርፍ መብራት ኃይል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ህንፃ በወቅቱ 47 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን በዋና መ/ቤትነት እያገለገለ ነው፡፡ የተለያዩ ድርጅቶችም በቢሮነት ተከራይተውታል። በቦሌ መንገድ እየተሰራ ያለው ባለ 14 ፎቅ ህንፃ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ይፈጃል ተብሏል፡፡ ሕንፃው ለንግድ ማዕከልነትና ለመኖሪያነት የሚያገለግል ነው፡፡ ዘመናዊ እርሻው ያለው በምዕራብ ጎጃም አዊ ዞን፣ በግምጃ ቤት ወረዳ በኢንጅባራ ከተማ “አየሁ እርሻ ልማት” አካባቢ ሲሆን በ17.5 ሚሊዮን ብር በ1000 ሄክታር ላይ  የተቋቋመው ነው፡፡ እርሻ ልማቱ በቆሎ፣ በርበሬና ሌሎች ሰብሎችም ያመርታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቡና ማልማትም ጀምሯል፡፡

በለገጣፎ ከተማ በ32 ሚሊዮን ብር የተቋቋመው አዲስ አሐዱ ፓኬጂንግ ፋብሪካ፤ ለኤክስፖርት ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን በምርት ጥራቱና በቀጠሮ አክባሪነቱ በመንግሥት እውቅናና ምስጋና በማግኘቱ በቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ መሸለሙንና ለ580 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ባለሀብቱ ተናግረዋል፡፡

አሐዱ ኩባንያ ከ20 ዓመት ያላሰለሰ ጥረትና ከፍተኛ ትግል በኋላ ከፍተኛ እውቅና ያገኘው ከሦስት ዓመት ወዲህ ሲገነባ በቆየውና ከሦስት ሳምንት በፊት በተመረቀው አሐዱክስ ፉድ ፕሮዳክትስ ኩባንያ ነው፡፡ አቶ ሰለሞን፣ ኢትዮጵያ፣ ጥራቱ በዓለም የታወቀ ስንዴ አምራች ሆና የስንዴ ውጤት የሆኑ የተለያዩ ብስኩቶች፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ… ከውጭ አገራት ስታስገባ ማየት በጣም ያስቆጫቸዋል፣ ያማቸዋል፡፡ መቼ ነው ይህን ከውጭ የሚገባ የስንዴ ምርት ተክተን ለግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ የምናድነው? መቼ ነው በአገራችን ስንዴ የተሰራ ምርት ወደ ውጭ አገር ልከን ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ የምናመጣው? በማለት ብዙ ጊዜ አስብ ነበር ይላሉ፡፡

አሁን ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ በመገንባት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ (36 ሚሊዮን ዶላር) በቢሾፍቱ ከተማ እጅግ ዘመናዊ የብስኩት፣ ፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ ገንብተው ራዕያቸውን በማሳካታቸው በጣም ደስ ብሏቸዋል፡፡ የጥራት ደረጃው ከፍተኛ የሆነ ለአገር ውስጥና ለዓለም ገበያ ምርት ለማቅረብ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ማሽነሪዎች ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን እጅግ ዘመናዊ ማሽነሪዎች ከኢጣሊያ ለመግዛት ቢያዙም፣ ማሽነሪዎቹን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መጠነኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ገጠማቸው፡፡ ስለዚህ አብሯቸው የሚሰራና የእውቀት ሽግግር የሚያመጣ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ለማግኘት በራሳቸውና በአማካሪ ድርጅታቸው በዲዌይት በኩል ፍለጋ ጀመሩ፡፡

በደቡብ አፍሪካ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ታዋቂ የሆነ ኩባንያ አብሯቸው ለመሥራት ፈቃደኛነቱን አሳየ። ከኩባንያው ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ እኔ ገንዘቡን እሰጣችኋለሁ፣ እናንተ ሥራውን ሥሩ አላቸው፡፡ የእውቀት ሽግግር የማያደርግ በመሆኑ ትተውት ሌላ መፈለግ ጀመሩ፡፡ ፍለጋቸው ሰምሮ በሰሜንና ደቡብ አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያና በአፍሪካ የካበተ ልምድና እውቀት ያለው የእንግሊዙ ኩባንያ “ቫሳሪ ግሎባል ፕሩፕ” በፈለጉት መንገድ አብሯቸው ለመሥራት ፈቃደኛ ስለሆነ፣ ከ7 ወር ድርድር በኋላ በ2013 (እኤአ) ቫሳሪ ግሩፕ አሐዱን ተቀላቅሎ አሐዱክስ ፉድ ፕሮዳክትስ አ.ማ ተቋቋመ፡፡

በቢሾፍቱ ከተማ የተሰራው ፋብሪካ ከኢጣሊያ የተገዙት ማሽነሪዎች ተገጥመውለትና ቫሳሪ ግሩፕ እውቀቱን ይዞ ማኔጅመንቱን ስለተቀላቀለ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያላቸው ብስኩቶች እያመረተ ነው፡፡ የአቶ ሰለሞን ዕቅድ የአገር ውስጥ ፍላጎት ካሟሉ በኋላ ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ቫሰሪ ግሩፕ ዓለም አቀፍ የገበያ ልምድ ስላለው በቀላሉ ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ያስችላቸዋል። ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት ለማድረግ የአይኤስኦ እና ሀሳብ (Hasab) ዓለም አቀፍ ሰርቲፊኬት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የአይኤስኦን ሰርቲፊኬት አግኝተዋል፡፡ የሀሳብን ሰርቲፊኬት ለማግኘት ደግሞ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ባለትዳርና የልጆች አባት ናቸው። ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ራሔል አሰፋ ጋር ትዳር የመሰረቱት የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ነው፡፡ በትዳር ቆይታቸው አንድ ልጅ ወልደዋል፡፡ ነገር ግን ስንት ልጆች እንዳላቸው ሲጠየቁ መልሳቸው አምስት ናቸው የሚል ነው፡፡ አራቱ ከአብራካቸው እንደተገኙ ልጆች የሚያሳድጓቸው ናቸው፡፡ ጓደኛቸው በሞት ሲለይ፣ እናት ልጆቹን ለማሳደግ አቅም ስለተሳናት ልጆቹን ወስደው እንደራሳቸው ልጆች እያሳደጉ ነው፡፡

አቶ ሰለሞን ለወ/ሮ ራሔል ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት አላቸው፡፡ ብዙ ኢትዮጵያዊ ባሎች የማያደርጉትን እሳቸው ህዝብ ፊት ቆመው ሚስታቸውን አመስግነዋል፤ አሞግሰዋል፡፡ ሚስቴ ባለቤቴም የቢዝነስ ሸሪኬም ናት ይላሉ። “ሁሉንም የፕሮጀክት ሥራ የምትመራው እሷ ናት፡፡ እጅግ በጣም ጠንካራ፣ ጎበዝ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ የማትል፣ የማቀርበውን አዲስ ሀሳብ ሁሌ የምትደግፍ ናት። እውነቴን ነው የምለው የህይወት ባልደረባዬ ብቻ ሳትሆን የቢዝነስ ባልደረባዬም ናት፡፡ ስለ እሷ ለመናገር ቃላት ያጥሩኛል፡፡ ስለ እሷ ከእኔ ይልቅ ሰራተኞቻችን ብዙ ማለት ይችላሉ፡፡ የእኔ ሥራ ከከፍተኛ አመራሮች ጋርና እውቀት ከሚያስተላልፉ ድርጅቶች ጋር ነው፡፡ ፕሮጀክቶችን እየተከታተለች ተግባራዊ የምታደርገው እሷ ናት፡፡ የዲዛይን መሠረታዊ እውቀት ስላላት ዕቃ መርጣ የምትገዛው፣ አስጭና የምታመጣው፣ ዲዛይኑ እንዲህ መሆን አለበት፣ እንዲህ ዓይነት ቀለም መቀባት አለባት …. የምትለው እሷ ናት፡፡ ….” በማለት አሞግሰዋቸዋል፡፡ወ/ሮ ራሔል ዋና መስሪያ ቤታቸው አሐዱ ኮምፕሌክስና የቢሾፍቱ ፋብሪካ ሲሰራ፣ ቱታ ለብሰውና ኬፕ አድርገው ከኮንስትራክሽን ሰራተኞች ጋር ይሰሩ እንደነበር ሰራተኞቻቸው ነግረውኛል። ከዚህም በላይ ሩህሩህና ደግ፣ ባልና ሚስቱ ሰውን በሰውነቱ፣ በእውቀትና በችሎታው እንጂ በጎሳ፣ በሃይማኖት በዝምድና የማይመለከቱ ስለሆነ በሁሉም ድርጅቶቻቸው ውስጥ የሁለቱ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው እንኳ እንደሌለ መስክረዋል፡፡

ለዚህ ነው የብስኩት ፋብሪካው በተመረቀበት ወቅት አቶ ሰለሞን “በረጅሙ የሰነቅነውን አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ግንባታ ሃሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከአጠገቤ ሳትለይ የግልና የቤተሰብ ህይወቷን መስዋዕት አድርጋ ከጎኔ ለቆመችው ታታሪ፣ ብርቱና ሁለገብ ውዷ ባለቤቴ በህዝብ ፊት ቆሜ ስመሰክርላትና ሳመሰግናት በሥራ አጋሮቻችን ስም ነው” በማለት የተናገሩት፡፡

አቶ ሰለሞን የሥራና የውጤት ሰው ስለሆኑ ያቀዱት ነገር ውጤታማ ሲሆን ያስደስታቸዋል፡፡ አንድ ሥራ ውጤት ከሌለው ምን ተሰራ ይባላል? ድካም ነው ትርፉ ይላሉ፡፡ ለሥራ የሚመርጡት ሰዓት የለም፡፡ ስራ ከበዛ አምሽተውና ማልደው በመግባት እንደሚሰሩ ሰራተኞቻቸው ነግረውኛል። ሌላው ባህርያቸው ደግሞ ከማንኛውም ሰው ጋር ተግባብተው መስራታቸው ነው፡፡ ትልቁ ደስታቸው ደግሞ ለወገኖቻቸው የስራ ዕድል መፍጠራቸውና አገራቸው በዕድገት ጎዳና ላይ ሆና ማየታቸው ነው፡፡

የአሐዱ ኩባንያ ባለቤቶች በማህበራዊ ተሳትፎአቸውም ይታወቃሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያዘው መሰረት ከሚያገኙት ትርፍ አስተዋጽኦ በማድረግ ነዳያንን ያበላሉ፤ ያለብሳሉ፡፡ በሚሰሩበት አካባቢ ላለው ህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ት/ቤት፣ ክሊኒክ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ መንገድ….. ይሰራሉ፡፡ በቅርቡ እንኳ በቢሾፍቱ ከተማ የብስኩት ፋብሪካው በተሰራበት አካባቢ ላሉ አርሶ አደሮች ከብት ማጠጫና ለመስኖ የሚሆን ውሃ ማጠራቀሚያ ገንብተዋል፤ መምህራን የወደፊቱን አገር ተረካቢ ትውልድ ቀራጭ በመሆናቸው ለእነሱ ትልቅ ክብር አላቸው፡፡ ስለዚህ ለመምህራንና ለተማሪዎች ክብር ሲሉ በቢሾፍቱ ከተማ በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ነጥብ (4) ያመጡ ተማሪዎችን ፎቶግራፍ የያዘ አደባባይ አሠርተው ነገ ይመረቃል፡፡ ለሁለቱ ግንባታዎች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣታቸው ታውቋል፡፡ባለሀብቱ የቢሮክራሲ፣ የባንክ አገልግሎት፣ የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ፣ የኢንተርኔት… የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው ያሉትም በአገሪቷ በእኩል ደረጃ እንዳልተሰራጩ በመጥቀስ ለአብነት በቢሾፍቱ ከተማ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት አለ ለማለት እንደማያስደፍር ገልጸዋል፡፡የአሐዱ ኩባንያ ባለቤቶች በ10ሺህ ብር ካፒታል ጀምረው በአሁኑ ወቅት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ካፒታል አላቸው፡፡ ሰራተኞቹም 2500 ደርሰዋል፡፡ ምርቶቻቸውን የሚያከፋፍሉበት 40 መካከለኛና ትላልቅ መኪኖች ሲኖሯቸው፣ ወደፊትም ለወገኖቻቸውና ለአገር ዕድገት አስተዋጽኦ በሚያደርጉ መስኮች የመሰማራት ዕቅድ አላቸው፡፡ 

 

 

 

 

 

 

 

 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመብራት ችግር እየባሰበት መሆኑን መናገር ለቀባሪው አረዱት ይሆናል፡፡ በቀን ከሁለት እስከ አራት ጊዜ የሚቆራረጥበት ወቅት አለ፡፡ መብራት አለ ብለው እንጀራ ለመጋገር ሲዘጋጁ እልም ይላል፡፡ ይመጣል ብለው ሲጠባበቁ በዚያው ቀልጦ የሚያድርበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢ ሁለትና ሦስት ቀን ከዚያም ሲብስ ሳምንት፣ አስር ቀንና ከዚያም በላይ ጠፍቶ ሲቀር ነዋሪዎች “የመብራት ያለህ” እያሉ በየሚዲያው ይጮሃሉ፡፡ ይህ ችግር በዓመት አንዴ የሚከበሩ በዓላትንም አይፈራም፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ለዘመን መለወጫ እንጀራ ለመጋገር አብሲት ተጥሎ መብራት እንደጠፋ በማደሩ በዓሉን በግዢ እንጀራ ማክበራችን ትዝ ይለኛል፡፡

መንግሥትና መብራት ኃይል ችግሩ ሲነገራቸው አንዳንድ ጊዜ “ዕድገት የፈጠረው ችግር ነው፤” ሌላ ጊዜ ደግሞ “የኃይል ማነስ አይደለም፣ የማሰራጫ መስመሮች እርጅና ነው፣ በዚህ አካባቢ ያለው ትራንስፎርመር ፈንድቶ ነው” ይላሉ፡፡ በየአካባቢያችንም ብዙ ጊዜ ትራንስፎርመር ሲፈነዳ ሰምተናል፣ አይተናል፡፡

ክቡር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመገናኛና ኮሙኒኬሽን ክላስተር አስተባባሪና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚ/ር፣ ባለፈው እሁድ የትራንስፎርመር ማምረቻ ፋብሪካን ሲመርቁ ባደረጉት ንግግር፤ ከዓመት በኋላ ትራንስፎርመር በየመንገዱ እንደ ማስቲካ እንደማይፈነዳ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ደብረጽዮን ይህንን ያሉት በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ በፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የትራስፎርመር ፋብሪካ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያላቸው ትራንስፎርመሮች እያመረተ በመላ አገሪቱ ስለሚያሰራጭ ነው፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ የአገሪቱን የትራንስፎርመር ፍላጐት አሟልተው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡ የገለጹት የኢንዱስትሪው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ አሰፋ ዮሐንስ፣ በመላው ዓለም ቻይናም ሆነች አሜሪካ የሚጠቀሙት ትራንስፎርመር ፋብሪካቸው ከሚያመርተው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በቡራዩ ከተማ አስተዳደር በታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር በ350 ሚሊዮን ብር የተሠራው ፋብሪካ ለኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ፣ ማሰራጫና ለቁጠባ የሚያገለግሉ ልዩ ትራንስፎርመሮችን ያመርታል። በዓመት 10ሺህ ትራንስፎርመሮች ያመርታል፣ ይተክላል፡፡ የጥራት ደረጃው ዓለም አቀፍ መሆኑን ማን እንዳረጋገጠላቸው የተጠየቁት ሻለቃ አሰፋ፣ የጥራት ደረጃ የሚለካው በምርት ወቅት በሚጠቀሙት የግብአት ጥራት፣ በሚያልፍበት የምርት ሂደትና በዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ተፈትሾ (ቴስት) ተደርጐ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የምርታቸው የብቃት ደረጃ 99.7 መሆኑን፣ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ጥያቄ ስላቀረቡ ከዓመት በኋላ ለውጭ ገበያ እንደሚልኩ ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው 1‚200 ሠራተኞች ሲኖሩት አብዛኞቹ፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተመረቁ ወጣቶች ናቸው፡፡ በፋብሪካው የኢንሱሌሽን፣ የዋይንዲንግ (ሽቦ መጠምጠም)፣ የአሴምቢሊንግ (መገጣጠሚያ) የኦይሊንግና ቴስቲንግ ወርክሾፕ የሚሠሩ አሉ፡፡

በእያንዳንዱ ወርክሾፕ የተመደቡት ወጣቶች ሁለት ሁለት ሆነው ነው የሚሠሩት፡፡ ሊዲያ ተስፋማርያምና ኢዮብ ዳና በኢንሱሌሽን ወርክሾፕ ሲሠሩ ነው ያገኀኋቸው፡፡ ሊዲያ የ21 ዓመት ወጣት ስትሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተመርቃለች። ኢዮብ 23 ዓመቱ ሲሆን ከቲቪቲ ኮሌጅ የተመረቀ ቴክኒሻን ነው፡፡ የወጣቶቹ ሥራ በትራንስፎርመሩ የሚጠቀለሉት ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ሽቦዎች እንዳይገናኙ በየመስመሩ ልዩ ዓይነት ኦርጋኒክ ወረቀት ማስገባት ሲሆን  ወረቀቱ ሌላም አገልግሎት አለው፡፡ በትራንስፎርመሩ የሚጨመረውን ዘይት ይመጣል፡፡

በኮኔክሽን ወርክሾፕ ሲሠሩ ያገኘኋቸው መቅደስና ታደሰ ጂጌ ኤሌክትሪሻኖች ናቸው፡፡ የ24 ዓመቷ መቅደስ ከወሊሶ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ነው የጨረሰችው፡፡ ታደሰም የ24 ዓመት ወጣት ሲሆን ከጂማ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተመርቋል፡፡ የወጣቶቹ ሥራ ከኃይል ማሰራጫ የሚመጣውን ኃይል ተቀብሎ ወደ ትራንስፎርመሩ የሚያደርሰውን ሽቦ መትከል ነው፡፡ በዚህ ዓይነት በሁሉም ወርክሾፖች ወጣቶች ተመድበው እየሠሩ ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

በአዲስ አበባ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ማርች 23 እና 24/ በምህጻረ FIGO የተሰኘው አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት በ8ኛው አህጉራዊ ስብሰባው ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥን በመከላከል ረገድ ምን ገጽታ አለ ወደፊትስ ምን መደረግ ይገባዋል የሚል ውይይት በአዲስ አበባ አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ተሳታፊ ከነበሩት ውስጥ የደቡብ አፍሪካውንና የኡጋንዳውን ተወካይ በአገራቸው ስላለው ሁኔታ ሀሳብ እንዲሰጡ አነጋግረናቸዋል፡፡ በዚሁ አህጉራዊ ስብሰባ ላይ ከተነሱ ነጥቦች የምናስነብባችሁ እውነታ በዚህ እትም ተካቶአል፡፡ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥ በተለይም በአፍሪካ አነጋጋሪነቱ ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ ምንም እንኩዋን ሀገራቱ እንደ አመቺነቱ የየራሳቸውን የአሰራር ደንብ ቢቀርጹም አሁንም በህብረተሰቡ ዘንድ ጉዳት ሲከሰት መስተዋሉ አልቀረም፡፡ ይህንን የሚመሰክሩት ከየሀገራቱ የመጡ ባለሙያዎች ሲሆኑ የኡጋንዳው ተወካይ የሚከተለውን ብለዋል፡፡“...ዶክተር ቺክ ጎምቸልስ እባላለሁ፡፡ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና እስፔሸሊስት እንዲሁም በኡጋንዳ የፅንስ እና የማህፀን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ነኝ፡፡ ፅንስ ማቋረጥ በኡጋንዳ በልማድ ሲሰራ የቆየ እጅግ ጎጂ ነገር ነው፡፡ በማህፀን ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን በመጨመር እንዲሁም የተለያዩ ኬሚካሎችን በመውሰድ ጭምር የተፀነሰውን የመግደል ስራ ነው የሚሰሩት፡፡ ምንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች ፅንስን ማቋረጥ የተለመደ ነገር ቢሆንም አብዛኛው ድርጊት ግን ጎጂ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ በኡጋንዳ ሴቶች በተለያየ መንገድ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ፅንስን ማቋረጣቸው በህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሲያስከትል ቆይቷል፡፡ በየአመቱም 300,000/ ያህል ጥንቃቄ የጎደለው ፅንስን ማቋረጥ የሚኖር ሲሆን ይህም  በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛው ቁጥር ነው፡፡ፅንስን ማቋረጥን በሚመለከት በኡጋንዳ በህግ የተደነገገ አሰራር አለው፡፡ ለዚያም መነሻ የሆነው አብዛኛው ፅንስን ማቋረጥ የሚሰራው ንፅህናውን ባልጠበቀ እና ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ በመሆኑ ነው፡፡ አብዛኞቹ የጤና ባለሙያዎች ፅንስን በማቋረጡ ሂደት በቂ ግንዛቤ አላቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ ጽንስን ማቋረጥ ግማሽ ያህሉ እውቀት ባላቸው ሰዎች የሚሰራ ሲሆን ግማሽ ያህሉ ግን በሴቶቹ በራሳቸው እንዲሁም በተለያዩ እውቀቱ በሌላቸው የቤተሰብ ወይንም የህብረተሰብ አባላት ነው፡፡ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ፅንሱን በሚያቋርጡበት ግዜ ሴቶቹ ለተለያየ ጉዳት ይጋለጣሉ፡፡ ደም መፍሰስ፣ ኢንፌክሽን፣ የማህፀን መቧጠጥ፣ መቁሰል የመሳሰሉት ሁሉ ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል ናቸው፡፡ በኡጋንዳ በቀን እስከ ስድስት ሴቶች ፅንስን በማቋረጥ ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል። በአመትም እስከ 4,200/ ሴቶች ጥንቃቄ በጎደለው ፅንስ ማቋረጥ ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል፡፡ አሁን ችግሩን ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ ነን፡፡

በእርግጥ ልንደርስ ካሰብንበት ቦታ ለመድረስ ገና ይቀረናል ነገር ግን የሴቶቹን ህይወት ለማዳን በምናደርገው እንቅስቃሴ የኡጋንዳ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድጋፍ እያደረገልን ሲሆን ጥሩ ጥሩ ፖሊሲዎች ተቀርፀዋል፡፡ በህጉም በኩል እንደገና የሚታዩ  ሚሻሻሉ ነገሮች ስለአሉ ሁኔታው  እየተሸሻለ ነው፡፡ ስለዚህም በወደፊቱ አሰራር ጉዳቱ እየቀነሰ እንደሚመጣ እሙን ነው፡፡

የምጨምረው የግል አስተያየቴን ነው በማለት ዶክተር ቺክ ጎምቸልስ የሚከተለውን ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡

“”....ያልተፈለገ እርግዝና አንድ ወንድና አንንዲት ሴት በፍቅር ተግባብተው የሚፈጥሩት ሲሆን በኋላ ግን የሴቷ ችግር ይሆናል፡፡ ከስነልቦና ጉዳቱ ባሻገር ወደ አካል ብሎም ህይወት እስከ ማጣት ድረስ ጉዳት የሚደርሰው በሴቷ ላይ ነው፡፡ ይህንን እንደ አንድ ትልቅ የሀገር ጉዳይ መመልከት ይገባናል፡፡ ሴቶች በወሲብ ግንኙት ወቅት እንዲወስኑ፣ መቼና ምን ያህል ልጆች እንደሚያስፈልግ፣ እርግዝናው እንደማያስፈልግ ሲታወቅ ምን ማድረግ እደሚገባ ምርጫ እንዲኖራቸው እና ከሚደርስባቸው ጉዳት እራሰቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡” ብለዋል፡፡

በማስከተል የጋበዝናቸው እንግዳ ከደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡  

“...ስሜ ኤኪ ሙስታንጋ ይባላል፡፡ የመጣሁት ከደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ፅንስ ማቋረጥ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ጥረት እያደረግን ነው፡፡ የቀድሞው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የዛሬ አፍሪካ ዩኒየን ቼር ፐርሰን የሆኑት ሰው ሴቶች ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ እንዲያደርጉ የተቻላቸውን ሁሉ አደርገዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት ህብረተሰቡም መብቱን አውቆ በጤና ተቋማት እንዲገለገል ባለሙያዎችም የእናቶችን መብት በማክበር እና ሙያውን በትክክል በመተግበር የሚችሉበትን አቅም በስልጠና እና በመሳሰሉት መንገዶች እየገነባን ነው፡፡ ስለሆነም ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ በሚከናወን ጽንስ ማቋረጥ ምክንያት በደቡብ አፍሪካ ህይወታቸውን የሚያጡ ሴቶች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ አሰራሩን በህግ የተደገፈ ለማድረግ ሕግ የወጣው በ1996 ዓም/ ሲሆን ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረው ግን በ1997 ዓም/ ነው፡፡ ቀደም ሲል ሴቶቹን በህክምና ለመርዳት የተስማሙት ሶስት ዶክተሮች ብቻ ሲሆኑ ህጉ ከወጣ በኋላ እና አሰራሩ ከተሸሻለ በኋላ ግን በርካታ ባለሙያዎች ህይወት እያዳኑ ነው፡፡

ባጠቃላይም በደቡብ አፍሪካ ከሚሞቱት እናቶች 30% የሚሆኑት ምክንያታቸው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ነበር፡፡ አሁን ግን በዚሁ ምክንያት የሚሞቱት ሴቶች 8% ብቻ ናቸው፡፡ 

በስተመጨረሻም ኤኪ ሙስታንጋ የተናገሩት...

“...በአፍሪካ ያለን ሰዎች ሁሉ ለሴቶች ክብር እና ከፍ ያለ ግምት ልንሰጣቸው ይገባናል፡፡ እነዚህ ሴቶች ትውልድን ለመተካት የሚችል ተፈጥሮ ያላቸው ብርቅዬዎች ናቸው፡፡ የሚጠቅማቸውን እና የሚጎዳቸውን ለይተው ስለሚያውቁ ሌሎች ሊወስኑላቸው አይገባቸውም፡፡ ስለዚህ እንስማቸው፡፡ ምርጫቸውንም እንጠብቅላቸው ሊያደርጉ የሚፈልጉት ነገር ካለም እንደግፋቸው፡፡” ብለዋል፡፡  

ጽንስን በመድሀኒት ማቋረጥ ጠቀሜታው በተለያየ መንገድ ሊመዘን ይችላል የሚለን  ኮንሰፕት የተሰኘው በ1989 ዓ/ም የተቋቋመው በተለይም የመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ  ባላቸው አገሮች የስነተዋልዶ ጤና በጥሩ ሁኔታ እንዲጠበቅ ለማድረግ ከየሀገራቱ ጋር የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡

በመድሀኒት አማካኝነት ጽንስን በተገቢው መንገድ ማቋረጥ በተለይም በታዳጊ ሀገሮች ያለው ጠቀሜታ የጎላ ቢሆንም ይላል ኮንሰፕት አንዳንድ አመቺ ያልሆኑ ነገሮች መከሰታቸው አልቀረም፡፡ ለምሳሌም የመድሀኒቶች ውድነት ከሚጠቀሱ መካከል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ጥራትና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ላይሆን ይችላል እንደ ኮንሰፕት እማኝነት፡፡ ከአምራቾች አኳያ ጉዳዩን ስንመለከተው ይላሉ መድሀኒቱን ለማዘዝ የፍላጉት መቀዝቀዝ ፈቃደኝነት ማጣትና በመድሀኒቱ ተጠቅሞ ተገቢውን አገልግሎት የማዳረስ ችሎታ በታዳጊ ሀገራቱ እየታየ አይደለም፡፡

በመድሀኒት አማካኝነት የሚደረግ ጽንስን ማቋረጥ ከ96-99% ውጤታማ ነው። ምናልባትም ውጤት አልባ ነው ቢባል 5% ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም ጎጂ ጎኑ መጠነኛ እና በፍጥነት ያልተፈለገውን ጽንስ ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ስለዚህ ህ/ሰቡ በቂ ግንዛቤው እንዲኖረው ማድረግና አገልግሎቱን ምቹ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡

በስብሰባው ላይ ከተሳተፉት ድርጅቶች ፓስ ፋይንደር አንዱ ሲሆን ልምዱን እንዳካፈለው ከሆነ ከ55 አመት በላይ ጽንስን በማቋረጥ ረገድ በሁለቱም  ማለትም ሕግ ባወጡም ባላወጡም ሀገራት ስራዎችን በመስራት ላይ ነው፡፡

እንደፓስ ፋይንደር እማኝነት ጽንስን ማቋረጥ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው በቀጥታ ከእናቶች ሞታ ጋር ስለተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከሴቶች የስነተዋልዶ ጤና ጋር በተገናኛ መሰረታዊ መብታ ቸው ሊከበር ስለሚገባውም ጭምር ነው።

በአለማችን ወደ 220/ሁለት መቶ ሀያ ሚሊዮን ሴቶች ዘመናዊ የሆነውን ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ አያገኙም፡፡ የእርግዝና መከላከያውን ቢያገኙ ኖሮ፡-

ያልተፈለገ እርግዝና ከ60% በላይ ይቀንሳል

የጨቅላ ሕጻናት ሞት በ44% ይቀንሳል

150,000 ያህል የእናቶች ሞት ይቀንሳል

600,000 ህጻናት እናቶቻቸውን በሞት አይነጠቁም፡፡ ይህ መረጃ ከ Women Care Global (WCG) የተገኝ ነው፡፡

ድርጅቱ እንደገለጸውም፡-

“...ስኬት የሚለካው በሴቶች ሕይወት መሻሻል እንጂ በገንዘብ ትርፍ አይደለም...”

በአለም አቀፍ ደረጃ በአመት በአማካይ 40/ ሚሊዮን የሚሆን ጽንስን የማቋረጥ ተግባር የሚፈጸም ሲሆን ከዚህም ከግማሽ በላይ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም፡፡

ወደ 90% የሚሆነው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ የሚፈጸመው በታዳጊ ሀገራት ነው፡፡

ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ለእናቶች ሞት በዋና ምክንያትነት ከሚጠቀሱት ከ5ቱ ገዳዮች አንዱ ነው፡፡

 

 

 

Published in ላንተና ላንቺ

 

 

 

              “መንግስት፤ እኔ ነኝ የአገሪቱ ደራሲ ይላል”

    ይኼንን ያለው አልበርት ካሙ ነው፡፡ አንድነት ግን በተጨባጩ አለም ሊገኝ የሚችል ነገር ሳይሆን ሲቀር፣ አርቲስቱ ተጨባጩን እውነታ በማፈራረስ ከፍርስራሹ ውስጥ የራሱን የምናባዊ አለም አንድነት እንዳለው አስመስሎ ያቀርበዋል፡፡ ይፈጥረዋል፡፡

“አንድነት በተለዋጭ አለም ይኸው እንዴት ውብ እንደሆነ” ብሎ ያቀርባል፡፡ እናም የፈጠረው አንድነት የተሳካ ከሆነ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ የፈለገ ምናባዊ ቢሆንም ግን ፈጠራው  ቀድሞ ከነበረው የእውነታ አለም የራቀ አይሆንም፡፡ ከራቀ የሚረዳውን አያገኝም፡፡ ካላገኘ፤ አንድነቱ የቱ ጋ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ግን ተሳካለት እንበል፡፡ ማለትም የፈጠረው ምናባዊ ጥበብ አንድነትን በሰው እና በፈጣሪ መሀል ወይንም በሰው እና በማንነቱ … መሀል ያሉትን ቲዎሪያዊ ጥያቄዎች ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደፈነ፡፡ እና ምን ይከተል? ሲፈለግ የነበረው የፈጠራ ጥግ ተደረሰ ተብሎ ፍለጋው ይቆማል?

አይቆምም፡፡ የፈለገ አይነት ስኬታማ ድርሰት ቢዋቀር የሰው ልጅ የአንድነት ፍላጐት አይረካም። ደራሲው ራሱ እንኳን የመጨረሻው የውበት (አንድነት) ጥግን ነክቻለሁ ካለ በኋላ የራሱን መጨረሻ ለመብለጥ ሌላ ድርሰት ይጽፋል፡፡ ህይወቱ እስኪያከትም ድረስ ውድድሩን አይገታም። … የሚወዳደረው ከራሱ ጋር ነው፡፡ ወይንም ከራስ ወዳድነቱ ጋር፡፡

ምናልባት ጥበበኝነት ከራስ ወዳድነትም ጋር የሚጣመርበት ስፍራ ሊታየን የሚችለው እዚህ ላይ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ማርሴል ፕሮስት፤ “In remembrance of the times past” በተባለው ዐብይ እና ትልቅ ስራው አንድነትን የፈለገበት መንገድ ወደራሱ የትዝታ አለም በመመነን ነው፡፡ ተጨባጩን አለም አፈራርሶ የእሱን ጠባብ የውስጥ ግዛት አለምን አሳክሎ በማብዛት ታላቅ ፈጠራን ሰራ፡፡ ከሰው ልጅ ጋር ራሱን “አንድ” ለማረግ የመረጠው መንገድ… የሰው ልጅን ሁሉ ወደ እሱ አተያይ በመቀየር ነው፡፡

ማርሴል ፕሮስት፤ ያደረገውን ያላደረገ ፈጣሪ በመሰረቱ የለም፡፡ የአንድነት ብቸኛ ፍቺ ነው የምንለው የሙሉኤ ኩሉው እውነታ ደራሲ (እግዚአብሔር) እንኳን… ሁሉንም ነገር የከወነው ከራሱ አልፋ እና ኦሜጋዊ አተያዩ አንፃር አይደል? የአንድነት ፍላጐት ከራስ ፍላጐት አንፃር እስከሆነ ድረስ ወደ ጠቅላይ ስምምነት የሚያደርስ ፈጠራ ሊኖር አይችልም፡፡

በዚህ ምክንያት የውበት ፍቅር፣ የእውነት ፍቅር ወይም የአንድነት ፍቅር ከራስ ወዳድነት ፍቅር ጋር ያልተከለሰበት ውበት ተሰርቶ  አያውቅም፡፡

ለምሳሌ ፍቅር ሁሉ አንድነት ነው፡፡ ወንድ እና ሴት አንድ ለመሆን ወደ ፍቅር ይገባሉ፡፡ ግን አንድነታቸው ተዋረድ አለው፡፡ በተለምዶ ወንዱ አንድ አድራጊው ሀይል ነኝ ብሎ ሊያምን ይችላል፡፡ “የእኔ ነሽ … ባለቤትሽ ነኝ” ይላታል‘ኮ አፍ አውጥቶ። የፍቅራችን የአንድነት ደራሲ እኔ ነኝ ማለቱም ነው፡፡ ነገሩ ፍቅር ነው፣ ውበት ነው፤ ግን ውበቱ የተቀረፀበት አንፃር አለው፡፡

ማን ነበረ፤ “We are too small in mind and body to possess other people without pride or to be possessed without humiliation” ያለው እንደዚያ ነው ነገሩ፡፡

ነገሩ ደግሞ ሰው የሚፈጥራቸው ጥበባዊም ይሁን መንግስታዊ አንድነቶች ውስጥ ግዙፍ እውነት ሆኖ ይገኛል፡፡ “እኔ ነኝ የሀገሪቷ ደራሲ ይላል” መንግስት፡፡ ባልዬው፤ “እኔ ነኝ የቤተሰቡ እራስ” እንደሚለው፡፡

የመጽሐፍ ደራሲውም፤ “እኔ ነኝ የድሮውን እውነታ ፈታትቼ በአዲስ መልክ ፈጥሬ ያዋቀርኩት” ይላል፡፡ በራሱ ለመኩራት ሲል ፈጠራውን የሚከውነውን ያህል የአንድነት ፍላጐትም በተፈጥሮው አድሮ ውበትን ለመጨበጥ ያነሳሳዋል፡፡ ግን “እኔ አንድነቱን ካልፈጠርኩት ሳይፈጠር ይቅር! ወይንም ቢፈጠርም ተፈጠረ ሊባል አይችልም” የሚለው ምክኒያት ዋናው የተግባሩ የመነሻ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡

በአንድ ድርሰትም ሆነ በአንድ የመንግሥት አስተዳደር ጥንቅቅ ያለ የአንድነት ንድፍ ሊገኝ የማይችለውም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ (ከመሰለኝ ደግሞ…!)

ህዝብና መንግስት መሀል ጭቆና የሚኖረው፣ መንግስት ራሱን እንደ ደራሲ ሲያይ ነው፡፡ መንግስትን የሚተካ ሌላ ደራሲ የሚነሳው ከበፊተኛው ድርሰት ራስ ወዳድነት ውስጥ ነው፡፡ ግን በዛው መጠን መዘንጋት የሌለበት አዲሱ ደራሲም አዲስ አንድነት ለማምጣት የሚጥረው ለህዝቡ ሲል ሳይሆን ከራሱ “Ego” (ፍላጎት) ተነስቶ ነው፡፡

ግን ማንም ደራሲ ቢመጣ፤ የቀደመውን ምናባዊ ድርሰት፣ በሌላ ምናባዊ አለም ቢለውጥ፣ ወይንም ተጨባጩን ቢሮክራሲ በሌላ አሻሻልኩ ቢል፣ ከራሱ እይታ አንፃር እስከሆነ ድረስ ጥቅሉ ውበት (አንድነት) አይጨበጥም፡፡

ባል ሚስቱ ጥላው ስትሄድ አልያም መንግስትን ህዝብ አልወድህም ሲለው…የፍቅሩ መቋረጥ ከሚቆረቁረው ይበልጥ ሚስት እሱን ትታው ሄዳ ሌላ ባል (ሌላ መንግስት) ማግኘቷ እንደማይቀር ማወቁ የስቃዩ እውነተኛ ምንጭ ነው፡፡

ብዙ የአንድነት አይነት አለ፡፡ ግን የራስ ወዳድነቱ አይነት አንድ ነው፡፡ “ሳዲስት” ከ “ማሶቺስት” ጋር አንድነት ይፈጥራሉ፡፡ ፍቅር ይመሰርታሉ፡፡ ህዝብን የሚሰድብ ደራሲን መጽሐፍ የሚገዛ፣ መሰደብ ከሚወድ ህዝብ … የገበያም ሆነ የመናበብ ትስስር ይፈጥራል፡፡ የፍቅር አይነት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እንክብካቤ እና ጥሩ ህይወት በምትፈልግ ሚስት እና ፍላጐቷን በሚያሟላ ባል መሀል የሚፈጠር አንድነት አለ፡፡ ግን አንድነቱ በጥል እና ባለመስማማት ይፈታል፡፡ አለመስማማት ማለት ሁለቱም የአንድነት መስራች አካሎች ራሳቸውን ማስቀደማቸው ግልፅ ሲወጣባቸው፣ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ሳያሳምን ሲቀር ነው፡፡

እስካሁን የተሰራው የሰው ልጅ የድርሰት መፅሐፍ ለምን አንድ ላይ ተደምሮ ትልቅ ውበት ማግኘት አልተቻለም? የሚል ጥያቄ ከመጣ መልሱ፡- የማንም የራስ ወዳድነት ንድፍ ከሌላው ጋር ቢደመር ትልቅ ራስ ወዳድነት እንጂ ትልቅ ውበት ወይንም ፍቅር አይወጣም፤ የሚል ይመስለኛል፡፡

ትልቅ ራስ ወዳዶች ትልቅ ጥበብን ይፈጥራሉ። በጥበቡ የሚስማማላቸው፣ በእነሱ እይታ መነፅር አለምን ለማየት ህዝቡ ወይንም ተደራሲያቸው እስከፈቀደላቸው ድረስ ሳይፈቅድ ሲቀር ሌላ ደራሲ የድሮውን አንድነት በራሱ አዲስ አተያይ ለውጦ እንዲያሳያቸው ይፈቅዳሉ፡፡ ሲፈቅዱ የወጣውን አውርደው የወረደውን አዲስ የአንድነት ደራሲ ያነግሳሉ፡፡

ትልቅ ራስ ወዳዶች ጥበብን ይፈጥራሉ፡፡ ራሳቸውን ከፈጣሪ፣ ከተፈጥሮ፣ ከስነምግባር ልዕለ ትርጉም ጋር ለማስተሳሰር ሲሉ፤ … ግን ለማሰር የሚሞክሩት በድርሰታቸው የደረሱትን ህዝብ ነው። ህዝብም ራስ ወዳድ ነው፡፡ ህዝብም ሰው ነው፡፡

ህዝብ ለመንግስት እንደ ሚስት ይመስላል፡፡ ባል ስልጣኑን ሲጭንባት ሚስት አሜን ብላ ትቀበላች፡፡ … ግን ጭነት ሲበዛባት ፍቅሯን (አንድነቷን) መጠርጠር ትጀምራለች፡፡ ጀምራ ከቀጠለች ባሏን ጥላ መሄዷ አይቀርም፡፡

ሚስቱ ጥላው የምትሄድ ባል፣ ህዝቡ ጥሎት የሚሄድ መንግስት ይበግናሉ፤ ይቃጠላሉ። የሚያቃጥላቸው ከህዝቡ ጋር የነበረው ፍቅር ከልባቸው አልወጣ ስለሚላቸው አይደለም፡፡ የሚያብከነክ ናቸው፡፡ ጥላ የሄደችው ሚስት ሌላ ባል ማግኘቷ እንደማይቀር በማወቃቸው ነው፡፡

በራስ ወዳድነት ላይ ተመስርተው የሚፈጠሩ አንድነቶች ሁሉ … አንድነት ሆነው የሚቆዩት ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ የተወሰነው ጊዜ ሲያልቅ … ሁሉም ፈጣሪ ነን ባዮች ወደ ተራነት ይመለሳሉ። መንግስትም ይቀየራል፣ ትዳርም ይፈርሳል፣ የገነነ ድርሰትም ከመፅሐፍ መደርደሪያ ላይ ወርዶ በሌላ ግነት ይተካል፡፡ የአንድነት ፅንሰ ሀሳብ ገናና የሚሆነው … የግለሰብ ራስ ወዳድነትን መጠን ያህል ነው፡፡

 

 

 

Published in ጥበብ
Page 4 of 19