በዕውቀቱና ኩንዴራ ምንና ምን ናቸው?
      
   (ካለፈው የቀጠለ)
ሰሞነኛው የልቦለድ ዕጣ - ፈንታ በተለይ ብዙ ለመፃፍ ተስፋ ላደረገ ሰው መብከንከኛው ነው። “ልቦለድ አልቆበለታል፣ መቀጠል አይችልም” የሚል መደምደሚያ ሲነገር በጉብዝናው ወራት እንደሚያውቁትና በመጨረሻው እንዳላማረ ጀግና በሀዘን ሆድ ይላወሳል፡፡ ልቦለድ በሞትና በሽረት መካከል ሆኖ የቀረበለት አማራጭ የጥቃት የመጨረሻው ጥግ ነው፡፡
ልቦለድ ከምናብ ጋር እንደተፋቀረ ወደ መቃብር ይውረድ? ወይስ ጊዜ የሰጠውን “ቅል” (ወግ Essay) አጉራህ - ጠናኝ ይበል?
እዚህ ላይ ልቦለድ ጊዜ የከዳው አሮጌ ጀግና ሆኖ ይታየኛል፡፡ ሰይፍ ቢታጠቅም መሰንዘሪያ ክንድ የከዳው …. ጋሻ ቢያነግብም መመከቻ ጡንቻው የሟሸሸ … ወጥመድ እንደገባ አንበሳ ከወዲያ ወዲህ እየተንጎማለለ በፊታውራሪ መሸሻ ግትር ባህርይ ወደ መሰበሪያው የሚያመራ …
“እጅህን ስጥ አለኝ ወግ
   እጅ ተይዞ ሊወሰድ፣
ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ?
አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ?”
ለመሆኑ ወግን የተጠለለ ልቦለድ በእርግጥ ልቦለድ ነው? ምናቡን የጣለ፣ ግርማውን የተገፈፈ፣ አሻግሮ ከማየት የተነፈገ፣ በደራሲው ኑዛዜ ላይ የተንጠላጠለ .. ፅሑፍ በእርግጥ ልቦለድ ነው? እርጋታውን ተነጥቆ የተንጦለጦለ፣ ለዛውን ተነፍጎ  ይዞ ወደመጣው ታሪክ የተገፈተረ፣ ጥላ ቢስ ከውካዋ … ልቦለድ ካለ ይቆጠራል? በዚያም በዚህም ብሎ ለልቦለድ የቀረበው አማራጭ ሁለት “ሞት” ነው? …
ባለፈው ፅሁፍ ያነሳው አጥኚ ዴቪድ ሺልድ፤ ልቦለድ ከሞት መዳን ካለበት የወግን ምስጢር ቁልፍ ሰብሮ በመግባት በመረጃው የመጠቀም ሽግግር ያስፈልገዋል ይላል፡፡ ቃል በቃል እንዲህ፡- “The novel facing extinction, it might need a transformation to survive; what digital natives call a hack”
ስለዚህ የልቦለድ ፀሐፊያን እነ ቶልስቶይን፣ እነ ዶስተየቭስኪን፣ እነ ዲከንስን ፣ እነ ሔሚንግዌይን፣ እነ ሀዲስ ዓለማየሁን፣ እነ በዓሉ ግርማንና ሌሎቹን ልቦለድ ደራሲያን ሳይሆን ነባሮቹን ወግ ፀሐፊያን ማጥናት ግዳቸው ነው፡፡ የእነ ሞንታኝን ወይም የእነ ጆዋን ዲድየን የወግ መፃፊያ ህግ መከተል፤ ምናብ ወለድ ታሪክ አያዋጣምና ወደ እውነታ መማተር፡፡ ሺልዲ አሁንም ቃል በቃል እንዲህ ይላል፡- “Story telling as self examination montaigne or Joan Didion, true life instead of fake life.”
ፈረንሳዊው የዘመናዊ ወግ ጀማሪ ሚካኤል ዴ ሞንታኝ (1533-1529) “ሙከራ” (Attempts) ብሎ ያስተዋወቀውን ወግ ሲገልፅ፤ “የእኔ ፍላጎት ሁሉም ሰው በመፅሐፌ ውስጥ እኔን እንደኔነቴ አድርጎ እንዲመለከተኝ ነው፡፡ ያለ ምንም መቀባባትና ሐፍረት” (My intention is that everyone see me in my book just as I am, without any shame or artifice) ብሏል፡፡ አክሎም፤ “መፅሐፌን ስታነቡ እኔን፣ እኔን ስታዩ መፅሐፌን ታውቃላችሁ” የሚል መደምደሚያ አስቀምጧል፡፡
እንግዲህ የዚህ ዘመን የልቦለድ ነፍስ አድን ባታሊዮን አባል ደራሲዎች የመጀመሪያ እርምጃቸው ኮሽታ እንደሰማች ኤሊ ወደ ውስጣቸው መግባት ነው፡፡ እዚያ ያገኙትን እውነት ያለ ሀፍረትና መቀባባት እንዳለ ማቅረብ፡፡
የቀረበውን (ድርሰቱ) ከአቅራቢው (ደራሲው) መለየት እስኪያቅት ድረስ አንደማድረግ፡፡ ከዚያ “ከሞንታኝ አመራር ጋር ወደፊት!” ማለት፡፡
ወግን “hack” ካደረጉ ልቦለድ ደራሲያን ውስጥ አውራውን ሚላን ኩንዴራን አንስተን ወደኛዎቹ እንደረደራለን፡፡ በትውልድ ቼክ በዜግነት ፈረንሳዊ የሆነው ኩንዴራ ደራሲነቱ “በዓመተ ፍዳ” እና “በአመተ ምህረት” የተከፈለ ነው፡፡ ኩንዴራ በሶሻሊዝም ንውዘት፣ ሀገሩ ቼክ ደግሞ በስታሊን መቅሰፍት ሥር የሚዳክሩበት ዘመን “አመተ ፍዳ” ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ስታሊን በቼክ ደራሲዎች ላይ የጣለውን ቅድመ ምርመራ በመቃወም ከሶሻሊስቱ አለም ጋር ከተቃቃረ በኋላ፣ ስደቱን ተከትሎ የተተካው ዘመን ደግሞ “ዓመተ ምህረቱ” ነው፡፡ በሁለተኛው አካፋይ ማለትም ከ1967 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ብቻ አስር ልቦለዶችን ፅፏል፡፡
የኩንዴራን ልቦለዶች፤ በተለይም “The Book of Laughter and Forgetting” ማንበብ ያልተደራጀው የኩንዴራ እሳቤ ውስጥ ገብቶ ዋዣቃ ባህር መቅዘፍ ነው፡፡ ቀጥ ያለ መንገድ የለም። ኩንዴራ እንደ አዲስ አበባ ሚኒባስ ታክሲዎች እያቆራረጠ ካንዱ እውነት ወደ ሌላው ሲያጋባን ይውላል፡፡ መንዱ ብቻ ሳይሆን “የአየር ሁኔታው” እጅግ ፈጣን፣ ተለዋዋጭ ነው፡፡ አንዳንድ የኩንዴራ “መንገዶች” እና “የአየር ሁኔታዎች” ተደጋግመው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የመፅሐፉ መጀመሪያ ላይ የሚተርከው የፕሮራግ ፖለቲከኞቹ ጉዳይ….
…. ጊዜው የካቲት 1948 ነው፡፡ ፕራግ ውስጥ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ፊት ኮሙኒስታዊ መሪ ክሌመንት ጎትዋልድ ወደ መድረክ ይወጣል። ጓዶቹ አጠገቡ ነበሩ። የአየር ሁኔታው ብርዳማ ስለነበር በቅርቡ የነበረው ክሌመንቲስ ኮፍያውን አውልቆ የጎትዋልድን ፀጉር አልባ ራስ ይሸፍናል። የፕሮፓጋንዳው ክፍል ጎትዋልድ ያንን ኮፍያ እንዳደረገ በጓደኞቹ ተከብቦ ፎቶ ያነሳዋል፡፡ ፎቶውን በብዙ መቶ ሺዎች አባዝቶ በትምህርት ቤት፣ ለመገናኛ ብዙሃን፣ ለሙዚየም ይበትነዋል፡፡ በፖስተር አሳትሞ በየአካባቢው ይለጥፈዋል፡፡
ከአራት ዓመት በኋላ የኮፍያው ባለቤት ክሌመንቲስ በአገር መክዳት ተወንጅሎ በስቅላት ይቀጣል፡፡ የፕሮፓጋንዳው ክፍል ወዲያውኑ ክሌመንቲስን ከታሪክ እንዲሁም ከሁሉም ፎቶግራፍ ላይ ያጠፋዋል፡፡ እዚያ የ1948ቱ ፎቶግራፍ ላይም ክሌመንቲስ ተሰርዞ በቦታው ላይ ግድግዳ ተተክቷል። የክሌመንቲስ ትውስታ ከራሱ ላይ ገፍፎ ጎትዋልድ ጭንቅላት ላይ ያኖረው ኮፍያው ብቻ ይሆናል፡፡
ኩንዴራ ይሄን የሚነግረን ከምናቡ አውጥቶ አይደለም፡፡ ታሪኩ የስታሊን እና የኬጂቢው ባለሥልጣን የኒኮላይ የሾቭ ነው፡፡ የሾቭ በአገር መክዳት ተወንጅሎ በስታሊን ከተገደለ በኋላ ከታሪክና ከፎቶግራፍ ሁሉ ተሰርዞ እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡ የኩንዴራ ትርጓሜ ሰውን ያህል ትልቅ ፍጡር በጉድጓዳ ጨርቅ ተተክቶ እንዲታየን ያደርጋል፡፡ ኩንዴራ ይሄንን ታሪክ እየመላለሰ በማምጣት የብዙ ትረካዎች ማንፀሪያ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ፍራንዝ ካፍካ የተሰኘውን ደራሲ የድርሰት መድረክ በጎትዋልድ የፖለቲካ መድረክ እየፈከረ የመፅሐፉ ክፍል ስድስት ላይ ያቀርብልናል፡፡
የኩንዴራ ልቦለዶች በፖለቲካ፣ በወሲብ፣ በፍቅር፣ በሥነ-ፅሑፍ እና በሌሎችም ጉዳዮች መጨናነቅ የበዛበትን የደራሲውን ነፍስ የሚወክሉ ናቸው፡፡ ብዙ ቁርጥራጭ ገጠመኞችና ሁናቴዎች ሳይሰደሩ በሥራው ውስጥ ይስተዋላሉ፡፡ ኩንዴራ እነዚህን ገጠመኞችና፣ ሁኔታዎች ተሰድረው መታወሳቸውን “የህይወት ታሪክ” ይለዋል። ምንም እንኳን ማህበራዊ ህይወት ውስጥ የሚኖረንን ቦታ እና የምንሻውን ደረጃ በማገናዘብ የአስፈላጊነትና ያለ አላስፈላጊነት ደረጃ ብናወጣላቸውም በራሳችን ጠንቅቀን አንረዳቸውም ይላል፡፡ የአንድ ደራሲ ኃላፊነት እነዚህን ቁርጥራጭ የህይወት ታሪክ ክፍሎች ሳይሰለቹ፣ ከተቻለ አስቂኝ አድርጎ ማቅረብ።
እዚህ ላይ ኩንዴራ ከኛው ደራሲ ከበዕውቀቱ ስዩም ጋር አይመሳሰልም? እንደውም አንድ ቀን አንቶኒ ሊሒን ከተሰኘ እንግሊዛዊ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ “ለምን ቀልዶችን እንደ አንድ የሥነ ፅሑፍ መሣሪያ አድርገህ ትጠቀማለህ?” የሚል፡፡ ሲመልስ፡
“ምናልባትም፣ በአፕሪል ዘ ፉል ቀን ስለተወለድኩ ይሆናል” ብሏል፡፡ በእርግጥም የተወለደው ኤፕሪል 1, 1929 ዓ.ም ነው፡፡
በዕውቀቱ ስዩም ሚላን ኩንዴራን እንዳነበበው አውቃለሁ፡፡ ሁለታችንንም በአንድ ወቅት ያስነበበን ሟቹ ደራሲ ደምሴ ፅጌ ነበር፡፡ በዕውቀቱ ኩንዴራን እንደወደደው አስታውሳለሁ፡፡ እሱን በወደደበት ዘመንም “መግባትና መውጣት” የተሰኘ ልቦለዱን ፅፏል፡፡ “መግባትና መውጣት” እንደ ኩንዴራ ሥራ ሁሉ “ወጋዊ ልቦለድ” (Essay Novel) ነው፣ ከዚህ ከቅርፅና ከአተራረክ ባሻገር በለዛም ሁለቱ ደራሲዎች የሚጋሩት ነገር አለ፡፡ በዕውቀቱ የተወለደው “በአፕሪል ዘ ፉል” ዕለት ይሁን፣ አይሁን ባይታወቅም እንደ ኩንዴራ ሁሉ ቀልድን የሥነ -ፅሀፉ እንድ አላባ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ ቀልድን የፖለቲካ ማሽሟጠጫ አድርገው ማቅረባቸውም ያመሳስላቸዋል። “መግባትና መውጣት” ውስጥ ካሉ ፖለቲካዊ ሽሙጦች ይሄን መጥቀስ ጥሩ ምሳሌ ነው….
… ልጁ ዝናብ አሳዶት ካፌ በረንዳ ላይ እየተጠለለ ነው፡፡ በኋላ ሲያባራ ከመሄድ ይልቅ ወደ ካፌው ገብቶ ይለምናል፡፡ ልጁ በተራኪው ሲገመገም፣ ሽሙጡ ብቅ ይላል፡፡ “ልጁን … ከላይ እስከ ታች ገመገምሁት፡፡ “የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚል ጥቅስ የተፃፈበት ለአዋቂ የሚሆን ቲ-ሸርት ለብሲ ነበር፡፡ በእርግጥ በጥቅሱ ላይ ያለው ‹እግዚዘ› የሚለው ቃል በእድፍ ስለ ተዋጠ “የጥበብ መጀመሪያ … ብሔርን መፍራት ነው” የሚለው ፅሁፍ ብቻ ይታያል፡፡”
ዳር ዳር ያልኩት ኩንዴራ የበዕውቀቱ መንገድ ጠራጊ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ኩካንዴራ በበዕውቀቱ የተወደደው የምርጫ አንድነት ስለነበራቸው ነው፡፡ ይሄንን ለማረጋገጥ የበዕውቀቱን “እንቅልፍ እና ዕድሜ”ን መመልከት ነው፡፡ በዕውቀቱ ይሄን ልቦለድ የፃፈው ኩንዴራን ሳያውቅ በፊት ነው። የሚገርመው ግን የሥራው ለዛ፣ ቅርፅ፣ የፍላጎት አዝማሚያ ከኩንዴራ “The Joke” ጋር መሣ ለመሣ የሚታይ ነው፡፡ “The Joke” ደግሞ አራት ተራኪዎች አንዱን ታሪክ ከየራሳቸው ጥግ እያዩ ቀለም የሚሰጡበት ስራ ነው፡፡ ቀልድን የልበሎለድ የሙያ ዕቃ አድርጎ ማቅረብም እዚህ የበዕውቀቱ ሥራ ላይ የተተገበረ ጉዳይ ነው፡፡ እንደውም ይሄ ልቦለድ በወጣ ሰሞን ሐያሲ አብደላ እዝራ “ሚዩዚክ ሜይ ዴይ” የሥነ ፅሑፍ መድረክ ላይ አንድ ጥናት አቅርቦ ነበር፡፡ የአብደላ ገለፃ እስካሁን አእምሮዬ ላይ ታትሞ አለ፡፡ እንዲህ ነበር ያለው፡- “እንቅልፍ እና እድሜ ውስጥ ቀልድ የሸፈነው የረጋ እንባ አለ፡፡ ላጥ ሲያደርጉት ሐዘን ኩልል ብሎ ይወርዳል፡፡”
የበዕውቀቱ ሁለቱ ሥራዎች ከምናብ ወጥቶ ወደ እውነታ መሸሸግ ብቸኛ አማራጩ ለሆነው ሰሞንኛ  ልቦለድ መሪ ኮከቦች ናቸው፡፡ እንደ ሰብአ ሰገሎች ከተከተላቸው አዲስ ተስፋ ወደተወለደበት የሥነ ፅሁፍ “ጋጣ” ያደርሱታል፡፡ ለመሆኑ “እንቅልፍ እና ዕድሜ” ሆነ “መግባትና መውጣት” ወጋዊ ልቦለድ መሆናቸውን በምን እናረጋግጣለን? እኔ ጥቂት ፍተሻ በማድረግ የደረስኩባቸው እውነቶች አሉ፡፡ በጥያቄ መልክ ለእናተ ላቅርብና እናንተም በየራሳችሁ ፍኖት ልትደርሱባቸው ሞክሩ፡-
“እንቅልፍ እና ዕድሜ” ውስጥ ተራኪዎች አሉ ብለናል፡
አንዱ ገጣሚ፤ ሌላኛው ሰዓሊ፤ ሶስተኛው የሥጋ መብል ጠል (Vegetarian) የሆነው የስነ - ልቦና አማካሪ ነው፡፡ ይሄ ከበዕውቀቱ ጋር በምን ይገናኛል? “መግባትና መውጣት” ላይ ያለው ተራኪ የጀርመንኛ ቋንቋ ተማሪ፣ ምዑዝ የሚባል ጓደኛ ያለው፣ ጆሮውን ታማሚ፣ ነገሮችን ገልብጦ የሚረዳ፣ …. ነው፡፡
እህስ? በዕውቀቱን በመፅሐፉ፣ መፅሐፉን በበዕውቀቱ ለይተን እናውቃለን? መፅሐፎቹ ውስጥ ቁርጥራጭ የህይወት ገጠመኞቹ እውነታን ወክለው ተቀምጠዋል? በህይወት የነበሩ ሰዎች ከበደ ሚካኤል፣ አፄ ቴዎድሮስ እና አባ አርጌኔስ ልቦለዱ ውስጥ መገኘታቸው ምንን ያመለክታል?...
(አማርኛ ልቦለድ፣ አማርኛ ወግን አጉራህ ጠናኝ ያለበት ሥራ የበዕውቀቱ ብቻ እንዳልነበር ባለፈው ፅሑፍ ጠቆም አድርገን ነበር፡፡ ነገር ግን ‹አንድ ሀረግ ሲመዙ ዱር ይነቀንቁ› ሆኖብን ጊዜና ቦታ እያጠረን ሄደ፡፡ ወደፊት ተለይቶ ባልተነገረ ዕለት ጉዳዩን ዳግም ቀስቅሰን ሌሎቹን ደራሲዎችና ሥራዎች ለመፈተሸ እንሞክራለን፡፡ እስከዚያው ለልቦለድ ትንሳኤ ያውርድ፡፡ አሜን!)

Published in ጥበብ
Saturday, 16 May 2015 11:29

የፍቅር ጥግ

ትዳር የዕድሜ ጉዳይ ሳይሆን ትክክለኛውን ሰው የማግኘት ጉዳይ ነው፡፡
ሶፍያ ቡሽ
ሚስቴ የልቤ ጓደኛ ናት፤ ያለ እሷ መኖርን ላስበው አልችልም፡፡  
ማት ዳሞን
 ትዳር ግሩም ተቋም ነው፡፡ ግን ማነው በተቋም ውስጥ መኖር የሚሻው?
ግሮቶ ማርክስ
ሴት ባሏን ለመለወጥ የማትሞክርበት ብቸኛ ወቅት ቢኖር የጫጉላ ሽርሽር ነው፡፡
ኢቫን ኢሳር
ሴት ለምንድን ነው 10 ዓመት ባሏን ለመለወጥ ከለፋች በኋላ “ይሄ ያገባሁት ወንድ አይደለም” ብላ የምታማርረው?
ባርባራ ስትሪላንድ
የትዳር ችግሩ በእያንዳንዱ ምሽት ፍቅር ከሰሩ በኋላ መፍረሱ ነው፡፡ እናም በእያንዳንዱ ጥዋት ከቁርስ በፊት እንደገና መገንባት አለበት፡፡
ጋብሬል ግራሽያ ማርኪውዝ
ትዳር ገነትም ገሃነምም አይደለም፤ የንስሃ ቦታ ነው፡፡
አብርሃም ሊንከን  
ደስተኛ ያልሆነ ትዳርን የሚፈጥረው የፍቅር እጦት ሳይሆነ የጓደኝነት (ወዳጅነት) እጦት ነው፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
ጥሩ ባል ጥሩ ሚስትን ይፈጥራል፡፡
ጆን ፍሎሪዮ
ፍቅረኛህ ከጋብቻ በኋላ እንዴት እንደምትይዝህ ለማወቅ ከፈለግህ ከትንሽ ወንድሟ ጋር ስታወራ አዳምጣት፡፡
ሳም ሊቨንሰን
የመጀመሪያውን ለፍቅር ብለህ ታገባለህ፡፡ ሁለተኛውን ለገንዘብ ብለህ፣ ሶስተኛውን ለጓደኝነት ስትል ታገባለህ፡፡
ጃኪ ኬኔዲ

Published in ጥበብ
Saturday, 16 May 2015 11:27

አዲስ ፍኖት

ላንቺ…
እንደምወድሽ ክጄ አላውቅም፡፡ ትላንት አልካድኩም። ዛሬም፣ ነገም አልክድም፡፡ ፍቅርሽ ሰውነት እንዲሰማኝ አድርጓል፡፡ ቀዩ ፊትሽ መስታወቴ ነው፡፡ ሳይሽ እራሴን አያለሁ፡፡ ሳወራሽ ‘ራሴን ያወራሁ ያክል ይሰማኛል፡፡ አፍንጫሽ ቁሞ ሳየው፤ ቅጥና ልክ ባጣው ያንቺ ፍቅር አንድ ቦታ ላይ ቁሞ የቀረው ማንነቴ ትውስ ይለኛል፡፡ በስጋዊ ህይወቴም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወቴ እንደ ጅግራ አንድ ቦታ ላይ ተገትሬ መቅረት እንደሌለብኝ አስባለሁ፡፡ ልቤ ውስጥ ለውጥ እያለ ሲጮህ እሰማዋለሁ፡፡
ወደፊት ባለመራመድ እንዳቆረ ውሃ ከጊዜ ብዛት መበከትና መሽተት እንዳልጀምር እሰጋለሁ፡፡ መፍትሄው መንቀሳቀስ፤ ‘ላይ ‘ታች ማለት መሆኑንም አምናለሁ፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ እየሮጥኩ ቢሆንም የበለጠ መቀልጠፍ፣ የበለጠ መሮጥ እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ ይሄ ደግሞ ግላዊ ህይወቴን ለማደርጀትና ኑሮ ላይ ለመጀገን የታሰበ ብቻ አይደለም፡፡ አንቺን ለማስደሰት ነው፡፡ እንድትመኪብኝና እንድትኮሪብኝም ለማድረግ ነው።
ህይወት ሁለት መልክ አላት፡፡ አንዱ መልክ እንደ ወርቅ የደመቀ እና እንደ አልማዝ የተወደደ ነው። ሌላው መልክ ጨረቃ አልባ እንደሆነ እና ከዋክብት እንዳደሙበት ሰማይ ጨለማ የወረሰው ነው፡፡ ድቅድቅ ጨለማ እንደነገሰበት ሌሊት ነው፡፡
ህይወት ለድምቀቱም ሆነ ለፍዘቱ ደንታ እንደማይኖራት ግልፅ ነው፡፡ ደንታ ያለን እኛ ነን። ህይወትን የመሾፈሩም ሆነ የማብረሩ ድርሻ የእኛ ነው፤ የእኛ የሰዎች! እና አንቺ ከጎኔ ስትሆኚ ተዋበች የአፄ ቴዎድሮስ ቀኝ እጅና መካሪ ዘካሪ እንደሆነችው፤ እኔም የልብ ልብ የምትሰጭኝ ያንቺ የልብ ወዳጅና እውነተኛ አፍቃሪ ለመሆን እጥራለሁ፡፡
ባንቺ እይታ ጥረቴ ሰምሮ ይሁን ከሽፎ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እውነተኛ አፍቃሪሽ ስለመሆኔ ግን በአስር ጣቶቼ ብቻ ሳይሆን በሃያ ጣቶቼ (በእግሬ ጭምር) እፈርማለሁ፡፡ ከማያዋጣው ወደሚያዋጣው፤ ከማይበጀው ወደሚበጀው፤ ከሚያከስረው ወደማያከስረው፣ ከማያተርፈው ወደሚያተርፈው ማንነት ባንቺ እመራለሁ፡፡ አንቺ ምሪኝ፤ እኔም እከተልሻለሁ፡፡ እውነቱን ልንገርሽ! ካንቺ ምሬት ወዴትም አልሄድም፡፡ እመኝኝ ከመራሽኝ መንገድ ትንሽ እንኳ ዘመም አልልም። ምክንያቱም እተማመንብሻለሁ። ምክንያቱም አብዝቼ እመካብሻለሁ፡፡
ከንፈሮችሽን ሣይ ከንፈሮቼን አስታውሳለሁ። መስታወት ፊት ቆሜም አያቸዋለሁ፡፡ “የቱ ውብ ነው?” ብዬ ለማወዳደር አይደለም፡፡ ያንዱን መጠን ከሌላው ጋር (የኔን ካንቺ ጋር) ለማስተያየት አይደለም፡፡ ምን ያህል ተገልበው ጥርሶቼን ለዕይታ አጋልጠዋል? ምን ያህል እርስ በርስ ተግባብተዋል? ወይም ምን ያህል አንድ ላይ ተሰፍተዋል? የሚለውን ለማወቅ ነው፡፡
ከንፈሮችሽን በአትኩሮት እመለከታለሁ፡፡ ሊፕስቲክ ለብሰው ወይም በቻፕስቲክ ወዝተው ሊሆን ይችላል። እሱን ከቁብም አልቆጥረውም። ጉዳዬ ከከንፈርሽ ልብሶች ሳይሆን ከዕርቃኖቹ ከንፈሮችሽ ነው፡፡
ስታወሪ ተመስጬ አያቸዋለሁ፡፡  ስትስቂ ወይም ፈገግ ስትይ አትኩሬ አያቸዋለሁ፡፡ ዝም ስትይም ከንፈሮችሽ እንደተሰበሰቡ በአይኔ ፎቶ አነሳቸዋለሁ።
ልንገርሽ?! … በሶስቱም ሁኔታ ላይ ሆነው ሳያቸው ያስደምሙኛል፡፡ ዝም ብለው መግጠማቸው መልዕክት ያለው ይመሰልኛል፡፡
ስታወሪ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከአንደበትሽ ከሚወጡት ቃላት በላይ የሚናገሩት ያላቸው ይመስላቸዋል፡፡ ስትስቂ ወይም ፈገግ ስትይ ወደ ቀኝና ግራ ጉንጮችሽ ሸርተት ሲሉ ለጉንጮችሽ ምስጢር ለማካፈል የሚንፏቀቁ (የሚሳቡ) ይመስላሉ፡፡
እኔ እረዳለሁ፡፡ ፍላጎታቸው ይገባኛል፡፡ እንቅስቃሴያቸው የሆነ ነገር ሹክ ይለኛል፡፡ መሳም ያማራቸው ይመስለኝና ልስማቸው እጓጓለሁ፡፡
ጥያቄ አለኝ ሊያ … ከምት ትወጂኛለሽ?! …
እየጠየኩሽ ያለሁት እንደ ዓሣ ለብለብ የሆነውን ለብለብ ፍቅር አይደለም፡፡ እየጠየኩሽ ያለሁት ስለእውነተኛውና ጥልቁ ፍቅር ነው፡፡ እንደመነኩሴ ቆሎ ብቻ እየበሉና ውሃ ብቻ እየጠጡ በአንድነት ተስማምቶ ለመኖር ስለሚስችለው ፍቅር!
እውነት ነው፤ አሁን እንዳጦዝኩት ጥብቁ ፍቅር ይቅርና “ተራው” ፍቅር ራሱ አለ ወይ? የሚሉ ጓደኞች አሉኝ፡፡ ፍቅር የለም የሚሉት ከመህበ አልቦ አይደለም። ዘመኑን ቃኝተው ነው፡፡ ወጣቱን አጥንተው ነው፡፡
እኔ ግን እላለሁ፤ ፍቅር አለ፡፡ ስለመኖሩም እኔ እንደ አብነት ልታይ እችላለሁ፡፡ ፍቅር የለበስኩ፤ ፍቅር የጎረስኩ፤ ስለ ፍቅር መኖር እርግጥነት በእርግጠኛነት ልታመን የምችል ህያው ምስክር ነኝ።
ፍቅር እንዴት እንዴት ያደርጋል? ይህን እኔ አላብራራውም፡፡ ስሜቱ ካለሽ አንቺ ብትነግሪኝ ደስ ይለኛል፡፡ ይህን ካደረግሽ እኔም ምናልባት በተራዬ የኔን ልነግርሽ እችላለሁ፡፡
ለአንባቢ፡- …
ሊያን የማውቃት ድሮ ነው፡፡ ድሮ! … የዛሬ ስንት ዓመት ልበላችሁ? ምናልባትም አስር ምናልባት አስራ አምስት፣ እንደዛ! (የቀንና የዓመት ቆጠራ የማይሳካልኝ ዜጋ ነኝ)፡፡
መጀመሪያ የተለየ ስሜት አልነበረኝም፡፡ ጓደኛዬ ነበረች፡፡ እንደማንኛውም ሴት ጓደኛ ጓደኛ! የማናወራው ነገር አልነበረም፡፡ ገና በተዋወቅን በመጀመሪያው ቀን ነው ሰፊ ጊዜ አብሮ ማሳለፍን አሃዱ ያልነው፡፡ ስለራሷ ብዙ ነገር አወራችልኝ፡፡ በጥሞና ሰማኋት፡፡ እሷ አፍ፤ እኔ ጆሮ ነበርን፡፡
ካወራችው ነገሮች ጥቂቱን አስታውሳለሁ፡፡ አንዱ የወሬያችን ርዕስ አባቷ ነበሩ፡፡ አባቷን በጣም ነው የምትወዳቸው፡፡ ፍቅር የተባለ ሁሉ ተጠቅልሎ ልቧ ውስጥ ተኝቷል፡፡ ፍቅር ልቧ ውስጥ ዳስ ጥሏል። የአባት ፍቅር …
ብዙ ሰዎች ብዙ ጊዜ ሲያወሩ የሚደመጡት ስለ እናት እና ስለ እናት ፍቅር ነው፡፡ እሷ ግን ስለ አባቷ አውርታ አትጠግብም፡፡ ስለአባቷ አክርራና አግና ስትናገር እናት የላትም ወይም የነበራት ሁሉ አትመስልም፡፡ አባቷ ወንድም፣ ሴትም፤ አባትም እናትም ሆነው የወለዷት ይመስላል፡፡
“አባቴ ለኔ ያልሆነው ነገር የለም” ትላለች፡፡
“አባቴ አምላኬ ነው” ለማለትም አትፈራም፡፡ በድፍረትና በእርግጠኝነት ትላለች፡፡
“እግዜር መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ኖረ ብለን ብናስብ እንኳን የሱ ውለታ የለብኝም፡፡ ያደረገልኝ ወይም ባለኝ ነገር ላይ የጨመረልኝ ነገር የለም፡፡ እግዜሬ አባቴ ነው፡፡”
አባቷ የጉልበት ሥራ እየሰሩ ነው ያሳደጓት። ባተሌ ነበሩ፡፡ አርፈው አያውቁም፡፡ ሥራም አይንቁም፡፡ ያገኙትን ሁሉ ይሰራሉ፡፡ ላባቸውን በብዙ አፍሰው፤ በጥቂቱ ያገኛሉ፡፡ ሱስ የለባቸውም። ሌላም ምንም አመል ስለሌለባቸው፤ ያገኙትን ይዘው ቤት ይገባሉ። እንደሰው መዝናናት ታይቷቸው አያውቅም፡፡ ራሳቸውን ለማስደሰት አንድም ቀን አስበው አያውቁም። ለራሳቸው ሱሪ ወይም ሸሚዝ ሳይቀይሩ ለሷ ቀሚስ ይገዛሉ። ለራሳቸው ማክያቶ እንኳን ሳይጠጡ እሷን ፊልም ይጋብዛሉ፡፡
እንደልጅም፣ እንደጓደኛም ነው የሚያኖሯት። ሌላ ወንድ ወይም ሴት የላቸው፡፡ እሷ ብቸኛዋ ልጃቸው ናት፡፡
“አባቴ” አለችኝ ሊያ “አባቴ ገና የራሱን ህይወት መኖር አልጀመረም፡፡ አሁንም ድረስ የሚኖረው ለኔ ነው፡፡ ውሎ የሚያድረው የኔን ውሎና አዳር ነው፡፡ ህይወቱ እኔ ነኝ፡፡”
“በጣም ይወዱሻል ማለት ነው?” ስል ጠየኳት። “በጣም እንጂ! በጣም! በአፍ ቃል አውጥቶ ነግሮኝ አያውቅም፡፡ ድርጊቱን ግን አነባለሁ፡፡ ድርጊቱን በማንበብ ብዙ ነገር እረዳለሁ፡፡ እንደሚወደኝና እንደሚያምነኝ ብቻ ሳይሆን እንደሚሞትልኝ ጭምር አውቃለሁ፡፡” አለች በእርግጠኝነት፡፡
“ከሚስቱ (ከእናቴ) ጋር ከተፋቱ ቆይቷል። እናቴን ብዙም አላውቃትም፡፡ እናትም አባትም የሆነኝ አባቴ ነው፡፡ እናቴ ሌላ ባል አግብታ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ትኖራለች፡፡ እዚህ እየኖረችም ብዙ አንገናኝም። አትፈልገኝም፡፡ አንዳንዴ እንገናኛለን። ብዙም ሳንጫወት እንለያያለን፡፡ እና የእናቴን ጣዕም አላውቅም። ብትሞት እንኳ የምደነግጥ ወይም የማዝን ወይም የማለቅስ አይመስለኝም፡፡ እናቴን አላውቅም፡፡ እናቴ ለኔ ባዳ ነች።” ብላ ተረከችልኝ።…
ሌላው የማስታውሰው ነገር ስለ ብርሃኑ ያወራችልኝን ነው፡፡ “ስጠራው ብሩ ነበር የሚለው፤ አሁን አሁን ግን ብርሃኑ እያልኩ ነው የማወራው። ብርሃኔ ብርሃኑ ሆኖ ነበር፡፡ የቶማስ ኤዲሰን ስሪ ከሆነው አምፖልና የእግዜር ስሪት ከሆኑት ፀሐይና ጨረቃ በላይ ነበር ለኔ ብርሃንነቱ። ይጠራልኝም ያበራኝም ነበር፡፡” አለችኝ፡፡ ዝም ብዬ ማድመጤን ቀጠልኩ፡፡
ፈገግ ብላ መልሣ ኮስተር አለች፡፡ ከፈገግታ ወደ መኮሳተር ስትሻገር መብራት የሄደ መሰለኝ፡፡
“ምን ያደርጋል … ሁሉም በነበር ቀረ” አለች ትክዝ ብላ “ተጣልታችሁ ነው?” አልኳት፡፡
“አይደለም፡፡ መጣላት አይባልም፡፡ መደባበር ሳይሆን አይቀርም”፡፡ ዞር ብላ፤ አየችኝ፡፡ እያዳመጥኩ እንደሆነ በአንገቴ ንቅናቄ ነግሬያት ፈገግ አልኩ፡፡ ፈገግታው ተጋባባት፡፡ ፈገግ ስትል ዙሪያ ገባችን በብርሃን ተጥለቀለቀ፡፡ አባቴን አይወደውም ነበር አለች፡፡
ከሱ ጋር ሆኜ ሳለ አባቴ ፈልጎኝ ከደወለልኝ “አባቴ ጠራኝ” ብየው እለየዋለሁ፡፡ ከብርሃኑ ጋር ተቀጣጥረን ከጨረስን በኋላ አባቴ ከኔ ጋር ሊያወራ ወይም ሊጫወት ፈልጎ ከሆነ ቀጠሮውን እሰርዛለሁ። ከአባቴ የማስቀድመው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ብርሃኑ በዚህ ይናደድ ነበር። አንድ ቀን ተማሮ አባቴን ሲሰድብ ሰማሁት፡፡ አባቴ በመሰደቡ ተብከነከንኩ፡፡ ከዛ በኋላ ፍቅሬ ቀነሰ፡፡ አባቴን ምንም እንዲጀካብኝ፤ ማንም እንዲናገርብኝ አልፈልግም፡፡ ይህና ሌላ ሌላም ምክንያትም እየተጨማመረ ለመለያየት በቃን” ገረመኝ። ለአባቷ ያላት ስሜት ጥንካሬና ጥልቀት ደነቀኝ፡፡
“ታድሏል” አልኩኝ አባቷን፡፡ እሷ ግን “እኔ ነኝ የታደልኩት” ትላለች፡፡
“እንደዚህ ዓይነት አባት በማግኘቴ እድለኛዋ እኔ ነኝ።”
*   *   *
ከሊያ ጋር በጓደኝነት ለብዙ ዓመታት አብረን ኖርን፡፡ በኋላ ግን ከመቀራረብም ከመግባባትም ብዛት ግንኙነታችን ወደ ፍቅር ተለወጠ፡፡ “መላመድ ፍቅር ነው” ይባል የለ?!
በጣም የምወዳት ሊያ ለፍቅር የማታመች ሆና አገኘኋት፡፡ ይህን ሳውቅ አዘንኩ፡፡ ሀዘኔ አንገት አስደፋኝ። ምን አደረገች?!
ወዳጀ ብዙ ናት፡፡ ዘመደ ብዙ ጠላው ቀጭን ነው ሳይሆን ወዳጀ ብዙ ፍቅሩ ቀጭን ነው ቢባል ሳይሻል አይቀርም፡፡ ብዙ የወንድና ሴት ጓደኞች አሏት፡፡ ሁሌም ቢዚ ናት፡፡ ለኔ ጊዜ አልሰጥ አለችኝ፡፡ ባይ ባይ አትለውጥም፡፡
ከኔ ጋር ገና ተገናኝተን ቁጭ ከማለቷ አባቷ ከደወሉ ጥላኝ ትሄዳለች፡፡ የአባቷን እንኳ እንደምንም ለመረዳት ሞክሬ ነበር፡፡ የባሰብኝ የሌሎቹ ነው፡፡ ላግኝሽ ብዬ ስደውልላት፡-
አበራን ቀጥሬዋለሁ፡፡ ማህሌትን አገኛታለሁ፡፡ ከተሸም ጋር ተቀጣጥረናል፡፡ ተሻለ ይጠብቀኛል፡፡
ሰለሞንን ላገኘው ነው፡፡ ….ትለኛለች፡፡ በድርጊቷ መናደድ ጀመርኩ፡፡ በመጨረሻ ምክንያቴን ሁሉ ነገሬ ተለየኋት፡፡ እየወደድኳት ተውኳት፡፡ ፍቅሬ አልወጣልኝም ነበር፡፡ ፍቅሬን አልጨረስኩም ነበር፡፡ ግን ምን ላድርግ? ከአቅሜ በላይ ሆነ፡፡ ብስጭቱን አልቻልኩትም፡፡ ሁሌ በንዴትና ቅናት ከመድበን አንደኛውኑ ተለያይቶ ናፍቆቱን መቻል ይሻላል ብዬ ወሰንኩ፡፡ ናፍቆቱን ግን በአግባቡ ልቆጣጠረው አልቻልኩም። በጣም ትናፍቀኝ ነበር፡፡ መደዋወሉን አቆምን። መገናኘቱን አቆምን፡፡ እና ሙሉ ለሙሉ የፍቅርን አጀንዳ ዘግተን ተጠፋፋን፡፡
*   *   *
ከሊያ ጋር ከተለያየን ከዓመት በኋላ መንገድ ላይ ተገናኘን፡፡
“በጣም እፈልግህ ነበር” አለችኝ፡፡
“አንድ ቀን አግኝቼህ ባጫውትህ ደስ ይለኝ ነበር፡፡”
ተገናኘን፡፡
“አጥፍቻለሁ” አለችኝ፡፡ “ለጥፋቴ ይቅርታ አድርግልኝና ጓደኝነታችንን ብንቀጥል ደስ ይለኛል፡፡”
ተስማማሁ፡፡
(ይቀጥላል)

Published in ልብ-ወለድ

 ከሰሞኑ በመፃሕፍት ገበያው የአጫጭር ወጎች ስብስብን በውስጣቸው ያቀፉ በመጠን ከሳ ያሉ የጥበብ ሥራዎች ጠፍተው በምትኩ፣ ለዓይን የከበዱ መፃህፍት(Fat books) ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ “የቄሳር እምባ” ከእነዚህ ሰሞነኛ መፃሕፍት መካከል ይመደባል። የ“ቄሳር እምባ” ደራሲ ሃብታሙ አለባቸው ስለ ቀድሞ የሀገራችን መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ፖለቲካዊ ሰብዕና፣የጦርነት ገድልና ውድቀት፣ውጥንቅጥ ማኅበራዊና ታሪካዊ ዳራን በ408 ገፆች በፈርጅ በፈርጁ እየመተረ ይተርክልናል፡፡
ደራሲው በእርግጥ በጥበብ አፍቃሪያን ዘንድ ጸጉረ ልውጥ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም “አውሮራ” በሚል ርዕስ በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት ላይ ያተኮረ ታሪካዊ ልብወለድ አቃምሶን፣ እጅ ነስተን ሳንጨርስ ነው ፈጥኖ  ይኼኛውን ጀባ ያለን፡፡ የአሁኑ መጽሐፍ የሚያውጠነጥንበት ጭብጥ ዝርያው ከ“አውሮራ” ጋር የማይገጥም ቢመስልም ዞሮ ዞሮ የአሁኗ ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ቁመና የወሰኑ ኩታ - ገጠም ነጥቦችን በሚያነሳባቸው አጋጣሚዎች ትስስሩን መመልከታችን አይቀርም፡፡
 ይህንን መጽሃፍ በተመለከተ በባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ እትም ላይ ሰለሞን ጓንጉል አባተ የተባሉ ጸሃፊ አጭር ምልከታቸውን እንዳኖሩ የሚታወስ ነው። ጸሃፊው በራሳቸው መንገድ መፅሃፉን የገለፁበትን አካሄድ እያከበርኩ ምልከታው ላይ ግን ብዙ መዳሰስ የሚገባቸውን ቋጥኝ ነጥቦች እንደዋዛ እየዳመጡ ማለፋቸውን ስለታዘብኩ ነው ይህንን ጽሑፍ ለመከተብ ብዕሬን ከወረቀት ጋር ያወዳጀሁት፡፡
የሰለሞን የምልከታ ፍሬ ሐሳብ የሚንደረደረው ከመጽሃፉ ጀርባ ላይ አስተያየታቸውን ያኖሩትን ሰዎች በመኮነን ነው፡፡ መጽሃፉ ገና ለሕትመት ከመብቃቱ በፊት የመመልከት ዕድሉን ካገኙት ሰዎች አንዱ ነበርኩ፡፡ በዚህም የተነሳ ስለመጽሃፉ የተሰማኝን ስሜት ይገልጸዋል ብዬ ያሰብኩትን ጥቂት ቁም ነገሮች አስፍሬያለሁ፡፡ የሰለሞን ጭንቀት አስተያየት ሰጪዎቹ ስለ ‘አውሮራ’ እንጂ ስለ‹የቄሳር እምባ’ የተረዱት ነገር የለም  የሚል ይመስላል። ግን ግምታቸውን  በአመክንዮ ሚዛን ስሰፍረው ውኃ አልቋጥር ስላለኝ ብዙም ማሰላሰል አልፈለግሁም፡፡
ጸሃፊው ሰለሞን “የቄሳር እምባን” የመሰለ አርበ - ሠፊ የጥበብ ሥራ ለመበለት የሄዱበት አካሄድ ጥድፊያ የተሞላበት ነው፡፡  መጽሃፉ ሊያስተላለፍ ከፈለገው ጭብጥ ይልቅ  የጥበብ ሥራው የሚፈረጅበት ዘውግ ላይ ብዙ ጊዜያቸውን ያጠፉ ይመስለኛል፡፡ በዚህም የተነሳ መፅሃፉ በውስጡ ያቀፋቸውን ደናግል ዕውነታዎች ሳያሳዩን፣ የማወቅ ጥማችንን  በእንጥልጥሉ እንዳስቀሩ ከማሳረጊያው ላይ ያደርሱናል፡፡
 የእኔ ሙግት የጥበብ ሥራው ከሚያስተላልፈው ጭብጥ አኳያ ሊገመገም ይገባል የሚል ነው፡፡ “የቄሳር እምባ” አያሌ ለውይይት የሚጋብዙ ፈርጀ ብዙ እውነታዎች ያሉት በመሆኑ በእነዚህ መሰሉ ጥቃቅን ነጥቦች ታጥሮ መታለፍ የለበትም ባይ ነኝ፡፡ በእርግጥ “የቄሳር እምባ” በይዘቱ ታሪካዊ ልብወለድ ከሚባለው ዘውግ  እንደሚመደብ ብዙ ማሳያዎች አሉት፡፡ ይህንን ነጥብ በደንብ ልዝለቅበት ብል አንድ ሌላ ጽሑፍ ስለሚወጣው በአጭሩ ገትቼዋለሁ፡፡ ታሪካዊ ልብወለዶች በአብዛኛው ስሜትን ሰቅዘው በሚይዙ ውጣ ውረዳዊ ኹነቶች የተተበተቡ ናቸው፡፡ ጥቅል ግባቸው ግን እዚህ በላይም አልፎ ይሄዳል፡፡ በውስጣቸው በመጥፎም ሆነ በበጎ የሚነሱ ታሪካዊ ዳራዎችን እርቃን በማስቀረት ቀሪው ትውልድ እንዲማርባቸው ፈለጉን ያመላክታሉ፡፡ “የቄሳር እምባ”ም ግብ ከእዚሁ ዓላማ ብዙም የራቀ አይደለም፡፡
መጽሃፉ ገና ከበር በደመነ ገጽታው ነው የሚቀበለን። እንደ አውላላ ሜዳ በተነጠፈ ወታደራዊ ሬንጀር ልብስ ላይ የኮሎኔሉ ቁጡ የፈራረሰ ገጽታ ታትሟል። ይህ የተኮማተረ ገጽታ ብዙ እውነታዎችን እንድንመዝ ይገፋፋናል፤ የፈራረሰ ሰብዕና፣ ርዕዮተ - ዓለም፣ ስልጣን… እያልን ስለ ፍቺው ለመጠበብ ከራሳችን ጋር ሙግት እንገጥማለን፡፡
ጥልቅ ዳሰሳ
ድብቅ እውነታዎችን የመኮርኮር አባዜ  
“የቄሳር እምባ” ሀገር ምድሩ  በውስጡ የሚያልጎመጉበትን ገመና አደባባይ ለማውጣት የሚታትር የጥበብ ሥራ ነው፡፡ ታላቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ በቄሳሩ መንበር ዙሪያ ከተሰለፉት ኃይሎች ጋር የነበረውን ቅርርብና ትስስር ከ“ኦሮማይ” በተለየ መልኩ ሊያሳየን ሞክሯል፡፡ ስለ በዓሉ ግርማ አሟሟት ከእዚህ ቀደም በየትኛውም የጥበብ ሥራዎች ላይ የማናገኘውን መላ ምት “የቄሳር እምባ” ያቀብለናል፡፡ በገጽ 9 ላይ ቄሳሩ በዓሉን በተመለከተ ከሻምበል ፍቅረሥላሴ ጋር  እንዲህ ያወጋሉ፡-
“የጓድ ተስፋዬ ልጆች ‘ደርጎች እንዴት አላችሁ?’  ብለው በዓሉን ጠየቁት፡፡ እሱ እየሰለሉት እንደሆነ አያውቅም፡፡ ’ጓድ ተስፋዬ ይህንን ሁሉ ሪፖርት አድርጎልኝ ነበር፡፡ ትንሽ ጊዜ ስጠው አልኩት። ምክንያቱም በኦሮማይ ምክንያት ሕዝቡ ‘የሥነ ጽሑፍ አንበሳ’ ብሎታል፡፡ እርምጃ ብንወስድበት የበለጠ ስም እናሰጠዋለን ብዬ ነበር ያዘገየሁት፡፡ ያው እንደሰማኸው ነው የወሬው ማዕበል። የእሱን መጽሐፍት ማንበብ ይቅርና የፊደል ስጦታ  ገበታ ገልጦ የማያውቀው ደንቆሮ ሁሉ ነው በዓሉ ሲል የነበረው”…
ይህንን መሰል  በምናብ የተለወሰ ታሪካዊ እውነታ ተመርኩዘን የታላቁ ደራሲ ሕልፈት መንስኤን ለማግኘት እናነፈንፋለን፡፡ አለፍ አለፍ እያልን በሄድን ቁጥር ብዥታውን ከሚያጠሩልን አመክንዮች ጋር መላተማችን የማይቀር ነው፡፡ ደራሲው ይህንን እውነታ በከሰተበት እጁ የቄሳሩን ጓዳ ጎድጓዳ  ከመበርበር ወደ ኋላ አይልም፡፡ ስለ ኮሎኔል መንግሥቱ ቤተሰባዊ ሕይወት ምናባዊ ፈጠራን ከአንዳንድ ተጨባጭ እውነታዎች ጋር በመለንቀጥ ከጅምሩ አንስቶ እስከ ማሳረጊያው  ግንዛቤያችንን ለማሳደግ ላይ ታች ይላል፡፡ በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ቤተሰባዊ ሕይወት ይቅርና ሰፊውን ሕዝብ የሚመለከቱ ሀገራዊ አጀንዳዎችን ማወቅ ብርቅ ነው፡፡ ይህ ብርቅ እውነታ ለጊዜው በ“የቄሳር እምባ” ላይ አደባባይ ሲሆን እንመለከታለን፡፡
በምኒልክ ቤተመንግሥት የመሸገው ብላቴና
መቶ አለቃ በላይነህ ደሴ ይባላል፡፡ የወ/ሮ ውባንቺ እህት ልጅ ነው፡፡ ደራሲው የውስጡን ንዳድ እንዲተነፍስለት በአፈቀላጤነት ያጨው ገፀ ባሕሪ ይህን ብልህ ብላቴና እንደሆነ ጥቂት ምዕራፎችን እንደገፋን እንደርስበታለን፡፡ መቶ አለቃ በላይነህ ዓይን መግባት የሚጀምረው ገጽ 97 ላይ ስለ ልግመት ኢትዮጵያ ብዕሩን ከወረቀት ማወዳጀት ሲጀምር ነው፡-
“ልግመት ኢትዮጵያ በአፈጣጠሩና በአስር ዓመታት ዝግመተ ለውጡ ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ተነጥሎ ሊመረመር አይችልም፡፡ ጓድ ጎርባቾቭ ‘በተቻለ መጠን ስህተቱን ከመዋቅሩ እንጅ ከግለሰቦች ድክመት አትፈልጉት’ ብለኸናል፡፡ በጊዜው ተቀብዬህ ነበር። አምጥቼ አገሬ ላይ ስሞክረው ግን አልሠራልኝም። ኮሎኔል መንግሥቱ የትጋት ኢትዮጵያ እምብርት የነበሩትን ያህል የልግመት ኢትዮጵያም ዋንኛ ምሶሶ ኾነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡”
ልግመት ኢትዮጵያ እና ትጋት ኢትዮጵያ በዲያሌክቲካል ጭውውት ማዶ ለማዶ  ተሰይመዋል። የቄሳሩ መንበረ ሥልጣን  ወገቡ ባልጠናበት በዚያ  በአፍላ ወቅት ሀገር ምድሩ ለትጋት አብዝቶ ይባትት ነበር፡፡ ሕዝብ “ሀገር ተወረረ ተነስ” ሲባል ሳያቅማማ ውድ ሕይወቱን ለመክፈል ይሽቀዳደማል፡፡ የደርግ አመራሮችም ቢሆኑ ለትጋት ኢትዮጵያ መገለጫዎች ነበሩ፡፡ ቄሳሩን የሚገዳደሩ የአስተዋይነትን እርፍ የጨበጡ የደርግ አመራሮችን መመልከት ብርቅ አልነበረም፡፡ ሲውል ሲያድር ግን ነገር መጣ፡፡
ሀገር ምድሩ የልግመትን ዳዋ ሙሉ ለሙሉ ለበሰ። ሰፊው ሕዝብ ሲለግም መሃሉ ዳር መሆን ጀመረ፡፡ “ፋኖ ተሰማራ” ብለው ነፍጥ አንግበው ደርግን ይወጉት የነበሩት ሻእብያና ሕውሃት መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ  ሆነላቸው፡፡ በላይነህ ደሴ የቄሳሩ በትረ ስልጣን እንክትክት ብሎ ለመሰባበር የሚጣደፍበትን ፍጥነት ልግመት ኢትዮጵያን እንደ አስኳል በመውሰድ ሌሎች ችግሮችን ከእዚህ አስኳል እየፈለፈለ ያስመለክተናል፡፡
ጥቁሩ ቄሳር፤ ልግመት ኢትዮጵያን ለመዋጋት የዘየዱት መላ መናኛ ነበር፡፡ በእርግጥም ቄሳሩ በውድቀታቸው ተዳፋት ላይ ይንደረደሩ ዘንድ  ዘንዶውን ትተው ግልግል እባቦችን  መግደል ነበረባቸው። ከመዋቅራዊ ለውጥ ይልቅ ግለሰቦችን በማሳደድ፣ በማሰር  እሳት ሊያጠፉ ሞክረዋል፡፡ ልብ ያላሉትና ትኩረት ያልሰጡት ዘንዶ(ልግመት) ግን በማሳረጊያው ላይ ከእግር እስከ ራሳቸው ሊውጣቸው  ጎሬውን ከፍቶ እየቀረባቸው በመጣ ቁጥር ራሳችንን በቄሳሩ ቦታ ሰይመን ታሪክን ልናርም፣ ልናርቅ መታተራችን የማይቀር ነው                                                                                                                                                                                               ጭልጥ ያለ ፖለቲካዊ አድርባይነት
“የቄሳር እምባ” በዚህ ሰብእና ላይ ምሕዋሩን ተክሎ ፍርዱን ለአንባቢ ይተዋል፡፡ በእርግጥ ይህ ሰብዕና የሀገራችን ፖለቲካ ልክፍት ከሆነ ውሎ አድሯል። ሌላው ይቅርና ነፍጥ አንስተው ደርግን ሲወጉት ከነበሩት ግምባሮች መካከል ሕወሓት ሳትቀር በእዚህ ረግረግ ሰብዕና እስከ አንገቷ ድረስ ሰጥማ እንደነበር ከታሪክ ድርሳናት ማጣቀስ ይቻላል፡፡ በተለይ በኤርትራ የነጻነት ጥያቄ ላይ ሕወሓት የአድርባይነት ዘይቤን ነው የተከተለችው፡፡
ደራሲው ግን ከእዚህ መሰሉ መዋቅራዊ ወይም ድርጅታዊ አድርባይነት ይልቅ ግለሰባዊ ሰብዕና ላይ በማተኮር የደርግ አገዛዝ ምን ያህል በፖለቲካ አድርባይነት እንደጨቀየ ሊያሳየን ሞክሯል፡፡ ከብዙ በጥቂቱ …..ከገጽ 205-206 በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምሥረታ ጉባኤ ላይ ካሳ ገብሬ የተባሉ ሰው የሚናገሩትን እንመልከት፡-
“እኛ የሰዎች ልጆች ሁላችንም ከአንድ ዓይነት ችሎታ ጋር እንደተፈጠርን ሳይንስ ይናገራል፡፡ እርግጥ ችሎታ ልናውቀው ወይም ላናውቀው እንችላለን፡፡ በእሳት ላይ ተረማምዶ ሃምሳ ሚሊዮንን ሕዝብ ለዚች ለተቀደሰች የዛሬዋ ቀን ማብቃት ግን የተለየ ችሎታ ነው። የተለየ ብቻም አይደለም፡፡ በጣም በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ የተጎናጸፉት ችሎታ ነው፡፡ ይህ ችሎታ በክፍለ ዘመን አንዴ የሚገለጥ የጥቂት ቦታዎች ክስተት ነው፡፡ ጠላትም ወዳጅም ይወቀው! እኛና አብዮታችን ይህ ችሎታ ባለው የሕዝብ ልጅ….እ…በቆራጡ …መሪ…እ…በጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም የምንመራ በመሆናችን ኩራታችን ነው….!!”
በቄሳሩ የአገዛዝ ስርዓት በአድርባይነት ማጥ ውስጥ የሰጠሙ ልክ እንደ ካሳ ገብሬ ዓይነት ብዙ ብኩን ሎሌ ካድሬዎች ነበሩ፡፡ የአድርባይነት ምንጩ አንድም ከባሕል፣ ከዕውቀትና ከዕምነት ልምድ የሚቀዳ ነው፡፡ ሃገር በአድርባይነት ውርጭ ስትመታ ጻዲቁን ከተኮናኙ መለየት ፈተና ይሆናል፡፡ አድርባይነት የአንድን ስርዓት ሁለንተናዊ ተፈጥሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመረዘና እያዳከመ የስርዓቱን ግብዐተ ቀብር የሚያፋጥን ክፉ ደዌ ነው። ደርግም ከእዚህ ደዌ የሚፈውስው አጥቶ ለዓመታት አጣጥሯል፡፡ ጣሩን ለመስማት ባለጊዜ የነበሩት ቄሳሩም ቢሆኑ  አርጩሜያቸውን ጠበቅ አድርገው መንበራቸውን በአይነ ቁራኛ ከመጠበቅ ውጪ የፈየዱት ነገር አልነበረም፡፡
የደራሲው ብዕር የለገመባቸው ኹነኛ ነጥቦች
በቂ ሽፋን ያልተሰጠው መፈንቀለ መንግሥት
በቄሳሩ አገዛዝ ላይ ያኮረፉት የሀገሪቱ ታላላቅ ጀነራሎች የደገሱት የመፈንቀለ መንግሥት ሴራ ሚዛናዊ ሽፋን አልተሰጠውም፡፡ ደራሲው የመንፈቅለ መንግሥቱን ሴራ ለማክሸፍ ከመንግሥት ወገን የተደረገውን ርብርቦሽ በዳሰሰበት ደረጃ ስለ መፍንቀለ መንግሥቱ ጠንሳሾች እንቅስቃሴ በቂ መረጃ ሊሰጠን አልከጀለም፡፡ በእነ ሜ.ጀነራል መርዕድ ንጉሴ እና ፋንታ በላይ የተመራው ቡድን በመከላከያ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሊያደርገው የሚችለውን ውይይት በተወሰነ መልኩ ማከል ተገቢ ነበር፡፡
የዘነበ ፈለቀ “ነበር ቁ. 2” የተሰኘው መፅሃፍ፣ በገጽ 197 ላይ ስለ መንፈቅለ መንግሥቱ ጠንሳሾች ይህንን ይነግረናል፡-
“ጀኔራል መርዕድ የሰብሳቢውን ወንበር አልለቅም ብለው እየመሩ፣ሜ/ጀኔራል ፋንታ ደግሞ ወንበሬ አልተለቀቀልኝም በሚል ኩርፊያ በረንዳ ላይ እየተንጎራደዱ፣ ሜ.ጀኔራል አበራ አበበ በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኙ ወታደርና ሲቪል ሠራተኞችን ሰብስበው “ጨቋኙ አምባገነኑ መንግሥት ወድቋል….”የሚል ይዘት ያለው ጽሑፍ አንብበው በምላሹ ደመቅ ያለ ጭብጨባ እየተቀበሉ ነበር …..”
በ“የቄሳር እምባ” ላይ ስለ መፈንቀለ መንግሥቱ ጠንሳሾች የዚህን ያህል ግንዛቤ የሚሰጥ አንቀጽ አናገኝም፡፡ ግራ እና ቀኝ የተሰለፉት ኃይሎች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ አልተዳሰሱም፡፡ ዳሰሳው ሚዛናዊ ቢሆን ኖሮ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይኖረው ነበር፡፡ አንድም እነዚያ ኃይሎች ቄሳሩን ገልብጠው የስልጣን እርከኑን ቢቆናጠጡ የአሁኗ ኢትዮጵያ ምን ልትሆን እንደምትችል አንባቢው ለመተንበይ ወይም ለመገመት የሚያስችለውን በቂ ግንዛቤ ያገኛል፡፡ ሌላው ታሪኩን የበለጠ ልብ አንጠልጣይና ሳቢ ለማድረግ የሚኖረውም አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ይሆን ነበር፡፡
የተዘነጋው የሕወሃት ማኒፌስቶ
 ደርግ በስልጣን ዘመኑ በተለይ እስከ ሽሬው ሽንፈት ድረስ ለሕወሓት የሰጠው ግምትና ትኩረት ተገቢ እንዳልነበረ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ይህ የደርግ ዳተኝነት “የቄሳር እምባ”ንም ተጋብቶበታል፡፡ የሕወሃትን ጥንስስ ዓላማ ደፈር ብሎ ሊያሳየን አልፈለገም፡፡ ሕወሓት በትግል ሒደት ውስጥ እንደየአስፈላጊነቱ ተገለባባጭ (Pragamatic) ፖለቲካ አጀንዳን ትከተል ነበር፡፡ በእርግጥ ይህ ታሪካዊ እውነታ ራሱን የቻለ ሌላ “የቄሳር እምባ” እንደሚወጣው እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ቢያንስ  ከሶስት እና ከአራት አንቀጽ ባልበለጠ ስለ ሕወሓት ፖለቲካዊ ቁመና በተለይ በእዚህ ሒደት ውስጥ ወሳኝ ድርሻ የነበረውን የ1975 ማኒፌስቶ መነካካት ቢቻል መልካም ነበር፡፡
በዘላለም ቁምላቸው ምህረቴ በተፃፈው “የኢትዮጵያዊነት እና የአማራነት መለያዎች ህብር በተሰኘው መጽሃፍ፣ ገፅ 278 ላይ ስለ 1975 ማኒፌስቶ እንዲህ ይላል፡-
“የ1975 ማኒፌስቶ  ገና ከመቅድሙ ሲጀመር እንዲህ ይላል፡- ትግራይ በጥንቱ ዘመን የአክሱም መንግሥት በመባል ይጠራ የነበረው ሲሆን ፣ያ ግዞት ከወደቀ በኋላ ግን በተለያዩ መጠሪያዎች ሲታወቅ የኖረ ቢሆንም፤(በዚህ ሁሉ ዘመን ውስጥ) ራሱን የቻለ ነጻ ግዛት(ኦቶኖመስ)ሆኖ ኖሯል፡፡ በዚህ ሰነድ ውስጥ፣በዚያው ገጽ ላይ በግርጌ ማስታወሻነት መልክ ደግሞ ፣የትግራይ ግዛት “ዓለምአቀፋዊ ድንበር” የወሰን ክልል ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በዚህም ካርታ መሠረትም፣ ኢህአዴግ በ1984 ስልጣን እንደጨበጠ ከወሎ እስከ ጎንደር የወሰዳቸው አካባቢዎች ሁሉ የትግራይ ክልል አካል ተደርገው ተቀምጠዋል፡፡”
ሕወሓት ከእዚህ ማኒፌስቶ የሚመነዘሩ ብዙ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ከድህረ ደርግ በኋላ ስትተገብር መታዘብ ችለናል፡፡ ማኒፌስቶው በሕወሓት የትጥቅ ትግል ውስጥ ብዙ ለትንተና የሚጋብዙ ታሪካዊ ኹነቶችን በውስጡ አቅፎ የያዘ ትልቅ የፖለቲካ አውድ ነበር፡፡ ይህንን አውድ ገሸሽ አድርጎ ስለትግል ሜዳው ውድቀትና ድል መተረክ ታሪኩን ሙሉ አያደርገውም፡፡ ስለ ቄሳር ውድቀት እየተረኩ ነገ ከነገ ወዲያ የቄሳሩን መንበር ስለሚረከብ የፖለቲካ  ኃይል ተፈጥሯዊ ባሕሪና ዓላማ ሳይዘግቡ ማለፍ ለተደራሲያን የሚያጎድለው ይበዛል፡፡
የሳሳ ልብ ሰቀላ
ደራሲው ለአንባቢ ልብ ሰቀላ ግድ የሰጠው አይመስልም፡፡ አብዛኛውን ትኩረቱን ያደረገው ፍሬ ያለው ነጥብ በማስተላለፍ ላይ በመሆኑ ልብ ሰቀላውን ዘንግቶታል፡፡ በእዚህም ምክንያት አብዛኞዎቹ ታሪኮች ልክ እንደ ጅረት ወጥ በሆነ መንገድ ነው የሚፈሱት፡፡ ይህም የታሪኮቹን መቋጫ ለመገመት ተደራሲያኑን ብዙም እንዳይቸገር አድርጎታል፡፡ አብዛኞቹ ታሪኮች አንባቢ ላይ የስሜት እቶን ለመርጨት የተመቹ ቢሆኑም በበቂ ሁኔታ መጎንጎን እና መቆስቆስ ይቀራቸዋል፡፡ በእዚህም የተነሳ ለብ ያለ ስሜት እየፈጠሩ ነው ከገጽ ገጽ የሚሻገሩት፡፡
መቶ አለቃ በላይነህ ደሴ የማስታወሻ ደብተሩን በሜ/ጀነራል መርዕድ ንጉሴ መኪና ውስጥ መርሳቱን ተከትሎ የተፈጠረው ዓይነት ጡዘት እንደ ትልቅ ጥንካሬ የሚወሰድ ነው፡፡ ይህንን ጡዘት ግን ሌሎች ጭብጦች ላይ ማጋባት ይቻል ነበር፡፡ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ በመንፈቅለ መንግሥቱ ትንቅንቅ ላይ ፣ቄሳሩ ከሃገር ለመውጣት የሚሰናዱበትን ትዕይንት ፣ በመቶ አለቃ በላይነህ እና በሐምራዊት የፍቅር ታሪክ ላይ የተሻለ ጡዘት ጨምሮ የልብ ሰቀላውን ደረጃ ከእዚህም በላይ ማሳደግ ይቻል ነበር፡፡
ጋዜጠኛና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ በቅርቡ በአዲስ አድማስ ላይ የዴቪድ ሺልድ ጥናታዊ ጽሑፍን ዋቢ በማድረግ “ልቦለድ በመጨረሻ ትንፋሽ ላይ” በሚል ርዕስ ግሩም መጣጥፉን አስነብቦን ነበር፡፡ የመጣጥፉ ፍሬ ሐሳብ የእውነታውን ዓለም ከግምት ያልጣፈ ወይም ያላካተተ የምናብ ፈጠራ አንባቢን የሚራብበት የመጨረሻ ዘመን ላይ ደርሰናል የሚል ነው፡፡ ረጅም ልብወለዶች በይዘታቸው ታሪክ ቀመስ ካልሆኑ በስተቀር የቀድሞውን ያህል ትኩረት የመስረቅ አቅም የላቸውም ይለናል፡፡
በእርግጥም ይህ የዴቪድ ሺልድ ጥናት እኛንም በደንብ ይገልጻናል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ፈጠራን የተላበሱ የረጅም ልብወለዶች አንባቢ ፊት ከነሳቸው ውለው አድረዋል፡፡ ሠፊ ተነባቢነት ያላቸው የጥበብ ሥራዎችን ዞር ብለን ስንፈትሻቸው ልክ እንደጥናቱ የእውነታውን ዓለም በውስጣቸው እንደደቀሉ እንደርስበታለን፡፡
ይህንን መሰሉ ታሪካዊ የረጅም ልብወለድ ደራሲ በተራቆተበት የጥበብ መስክ ላይ እንደ ደራሲ ሃብታሙ አለባቸው ዓይነት ጸሃፍት መከሰት ደግሞ ለጥበብ አፍቃሪያን እንደ ሲሳይ ነው የሚቆጠረው፡፡ ደራሲው በተለይም በአጭር የጊዜ ልዩነት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ መሰጠትን የሚጠይቁ ሁለት ቱባ የጥበብ ሥራዎችን ማበርከቱን ስንታዘብ ውዳሴያችንን መሸሸግ ይሳነናል፡፡
በአጠቃላይ ደራሲው ፀሃፍትን ተርቦ የኖረውን የረጅም ልብወለድ  ዘውግ መልሶ እንዲያንሰራራ ትልቅ የተስፋ ጭላንጭል የዘራ ይመስለኛል፡፡

Published in ጥበብ

 በመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች እንዲሁም ኤችአይቪን ጨምሮ በግብረ ስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚተላለፉ የተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ሰፊውን የስነተዋልዶ ጤና ችግር ይሸፍናሉ፡፡
በየአመቱ በአለማችን ላይ ቁጥራቸው 500/ ሚሊዮን የሚገመት ሰዎች በጎኖሪያ፣ ሲፊሊስ እንዲሁም ትራይኮሞኒያሲስ በሚባሉ በግብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት በሚተላለፉ የአባለዘር በሽታዎች እንደሚጠቁ 290/ ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶች ደግሞ በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ እንደሚያዙ የአለም የጤና ድርጅት በ2013/ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችን እና የአባላዘር በሽታዎችን በተመለከተ የኢንፌክሽኖቹን አይነት እና ምልክት እንዲሁም የትኛውን የመራቢያ አካል ያጠቃሉ በሚለው ዙሪያ አንድ ፅሁፍ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡
ዛሬም ሳምንት በይደር ያቆየነውን በመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችን እንዲሁም የአባላዘር በሽታዎችን እንዴት አስቀድሞ መከላከል ይቻላል? ተከስቶስ ሲገኝ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን እናያለን።
አብዛኞቹ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጡት ኢንፌክሽኖች ከግል ንፅህና ጉድለት ወይም ተገቢውን የንፅህና አጠባበቅ ባለመከተል የሚከሰቱ በመሆናቸው ተገቢውን የንፅህና አጠባበቅ በመከተል መከላከል እንደሚቻል በብራስ የእናቶች እና ህፃናት ሆስፒታል የፅንስና ማህፀን እስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር መብራቱ ይገልፃሉ፡፡
“...ባክቴሪያ በማንኛውም ሰአት ይከሰታል፡፡ የሚመጣውም የግል ንፅህና አጠባበቅ ስልትን ባለማወቅ ብቻ ነው፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ወደ ሰውነታችን የሚገቡ ባክቴሪያዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ባክቴሪያዎች በመነካካት እና በመተሻሸት ወይም በላብ አማካኝነት ወደ ሌላ የሰውነታችን ክፍል በመሄድ እና በመራባት ኢንፌክሽን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ነው እነዚህን በባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች የግል ንፅህናን መጠበቅ ብቻ መከላከል ይቻላል ያልኩት፡፡...”
የአልኮል መጠጦችን እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ ሱሶችን መቀነስ በግብረስጋ ግንኙነት ከሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች እና የአባላዘር በሽታዎች የሚኖረውን ተጋላጭነት መቀነስ ይቻላል፡፡ ይህም የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ መውሰድ እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ ሱሶችን መጠቀም በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት ሊደረጉ ከሚገባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች ስለሚያዘናጉ እንደሆነ ዶክተር መብራቱ ይናገራሉ፡፡
“...ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የግል ንፅህናን መጠበቅ እና ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነትን አለማድረግ ዋነኛው የመከላከያ መንገድ ነው፡፡ በግብረ ስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚከሰቱትን ኢንፌክሽኖች በተመለከተ ደግሞ ጥንቃቄ የተሞላበት የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ክፍተቶች በሚያጋጥሙበት ግዜ ኮንዶም መጠቀም በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ጥንቃቄ ማድረግ እና ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ አለመፍቀድ ነው። በተለያየ አጋጣሚ ክፍተት እንዲፈጠር ከሚያደርጉት ውስጥ ነገሮች መካከል አንዱ ሱሰኝነት ነው፡፡ መጠጥ፣ ጫት እና ሌሎች ሱሶችም አሉ እነዚህ ሱሶች ነገሮችን የማገናዘብ አቅምን ስለሚያጠፉ ከግንዛቤ ውጪ የሆኑ ስሜታዊ ነገሮችን ለማድረግ ሊገፋፉ እና ሊያደፋፍሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ከእነዚ ሱሶች መራቅ ተገቢ ነው፡፡...”
በግብረ ስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚከሰቱትን ኢንፌክሽኖች በተመለከተ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል ያሉትም አለ፡፡
“...ግብረስጋ ግንኙነት ላይ አሁንም ደግሜ ትኩረት እንዲሰጥበት እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው ትዳር ከያዘ በኋላ ከትዳሩ ውጪ ሌላ ቦታ መሄድ የለበትም። ያ ትዳርም ጤናማ ትዳር መሆን አለበት፡፡ በዚህ በምንነጋገርበት የጤና ጉዳይም ይሁን በሌላ ጤናማ እና ሰላማዊ የትዳር ህይወት እንዲኖረን ከፈለግን እነዚህ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡...”
ቀደም ሲል ከተጠቀሱት የመከካላከያ መንገዶች በተጨማሪ የአመጋገብ ስርአታችን በሽታን በመከላከል እረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል  ባይ ናቸው ዶክተር መብራቱ፡፡  
“...ለሰው ልጅ ዋነው መድሀኒት ምግብ ነው፡፡ በተቻለ መጠን ከሁሉም የምግብ አይነት ትንሽ ትንሽ መመገብ ያስፈልጋል፡፡ በእኛ ሀገር በባህል ስጋን አዘውትሮ መመገብ ልክ እንደ ጤነኛ የአመጋገብ ስርአት ይወሰዳል፡፡ ነገርግን ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ስጋ ከፍተኛ የሆነ ፕሮቲን ስላለው ለሰውነታችን ጠቃሚ ቢሆንም ሌሎችንም የምግብ አይነቶች መመገብ ሰውነታችን ብዙ አይነት ንጥረገነሮችን በተመጣጠነ መልኩ እንዲያገኝ ያደርጋል። ስለዚህ በእለት ተእለት አመጋገባችን ላይ ከሁሉም የምግብ አይነቶች ትንሽ ትንሽ ማካተት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይ ቫይታሚን ሊሰጡ የሚችሉ አትክልት እና ፍራፍሬ ምግቦችን ማዘውተር ይመረጣል፡፡
በሀገራችን ውድ ያልሆኑ ብዙ የአትክልት እና ፍራፍሬ አይነቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጎመንን መጥቀስ ይቻላል። ጎመን በጣም ውድ አይደለም ግን ብዙ ሰው ከጎመን ይልቅ ውድ የሆነውን ስጋን ይመርጣል፡፡ ልክ እንደ እስፒናች፣ ቲማቲም፣ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ብርቱካን እና ሙዝ ያሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎች በውስጣቸው ከፍተኛ የቫይታሚን እንዲሁም የአይረን መጠን ስላላቸው ጠቀሜታቸው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ሙዝን ብንመለከት ሙዝ በውስጡ ካልሺየም፣ አይረን  እና ቫይታሚን ስላለው ከፍተኛ ሀይል ይሰጣል፡፡ ለዚህ ነው እስፖርት የሚሰሩ ሰዎች ሙዝን የሚያዘወትሩት። ስለዚህ መጀመሪያ ፋርማሲ ሄዶ መድሀኒት ከመግዛት ይልቅ ምግብ ላይ ማተኮር ተገቢ ይመስለኛል፡፡...”
በእርግዝና ግዜ የሰውነት የበሽታ መከላከል አቅም ስለሚቀንስ እርጉዝ ሴቶች ለእነዚህ ኢንፌክሽኖች የሚኖራቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው ይላሉ ዶክተር፡፡
“...እርጉዞች እና ወላድ ሴቶች ለእንደዚህ አይነት ኢንፌክሽኖች የበለጠ ተጋላጮች ናቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በእርግዝና ወቅት የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም በእጅጉ ስለሚቀንስ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ እና የእርግዝና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ሰአት እርግዝናን እንዲሁም በአጠቃላይ ሌሎች የጤና ጉዳዮችን በተመለከተ ብዙ ፅሁፎች እየወጡ ነው ስለዚህ እነሱንም ማንበብ ጥሩ ነው፡፡ ነገርግን አንዳንድ ግዜ ከሙያ ውጪ የሚነበብ ነገር በጣም ሊያደናግር እና ሊያስደነግጥ ስለሚችል ጥያቄ ሲኖር ከባለሙያ ጋር መመካከር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ በሚያነቡት ነገር ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡...”
አንዳንድ ግዜ ይህ አይነቱ ችግር በባለትዳሮች ላይ ሲከሰት ባል ሚስትን ሚስት ባሏን ለችግሩ ተጠያቂ አድርገው አንዳቸው አንዳቸውን ሲወቅሱ ይስተዋላል። ለመሆኑ እንዲህ አይነት ኢንፌክሽኖች በአንድ ወገን ብቻ የሚከሰቱ ናቸው ወይንስ ሁለቱንም ፆታ በእኩል ያጠቃሉ? ስንል ላነሳንቸው ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡   
“...ሴቷ ብቻ የምትጠቃ ከሆነ ይህንን ነገር ማን አመጣው? የሄ ነገር ከየት መጣ? በግረስጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ነው ካልን አስተላላፊ ከሌለ የሚተላለፍበት ሰው እንዴት ሊይዘው ይችላል? ስለዚህ ለዚህ አጭሩ መልስ ሁለቱም ፆታዎች በእኩል ሊጎዱ እና ሊጠቁ ይችላሉ ነው፡፡...”
እንዲህ አይነት ኢንፌክሽኖች ወይም ተመሳሳይ የጤና ችግር ሲያጋጥም የህክምና ተቋም እስኪደርሱ አንዳንድ ህመሙን ሊቀንሱ የሚችሉ ነገሮችን ከማድረግ ባሻገር ያለ ሀኪም ትእዛዝ መድሀኒት መውሰድ ለሌላ ችግር ሊዳርግ ይችላል ይላሉ ባለሙያው፡፡
“...ህክምናውን በተመለከተ ያሉት ነገሮች ለባለሙያ ቢተው ጥሩ ነው፡፡ እራስን በእራስ ማከም ፈፅሞ አይመከርም፡፡ በዚህ ጉዳይ እረጅም አመት የተማሩ እና በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ከባለሙያዎቹ ጋር ተመካክሮ መድሀኒት መውሰድ ነው እንጂ እራስን በራስ ማከም የበለጠ አደጋ አለው፡፡ መድሀኒት በመድሀኒትነቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ የጎንዮሽ ጉዳትም እንዳሉት መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህ ህክምናውን በተመለከተ ለባለሙያ መተው ጥሩ ነው፡፡...”
ነገር ግን ይላሉ ዶክተር፡-
“...ነገር ግን ህክምና ጋር እስኪደርሱ ድረስ ለጊዜው የሚደረጉ አንዳንድ  ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ፈንገስ እና ተመሳሳይ ኢንፌክሽኖች ተከስተው ከሆነ በጨው ውሀ ወይንም በሎሚ ውሀ መታጠብ ሀኪም ጋር እስኪደረስ ድረስ ትንሽ ትግስት እና ፋታ ይሰጣል፡፡...”
የዛሬውን ፅሁፍ የምናጠቃልለው ዶክተር መብራቱ በመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችን እንዲሁም የአባላዘር በሽታዎችን በተመለከተ መታወቅ አለበት ብለው በሚያስተላልፉት መልዕክት ነው፡፡
“...እንዲህ አይነት የጤና ችግር በሚፈጠርበት ግዜ ወንዶች ሴቶቹን መኮነን ወይም ሴቶች ወንዶቹን መኮነን የለባቸውም፡፡ ሁለቱም አብረው የሚኖሩ ጥንዶች ናቸው። እርስ በእርስ በመተሳሰብ ምን ሆኖ ይሆን? ምን ሆና ይሆን? የሚለውን ቀና ነገር በማሰብ እስከ መጨረሻው ድረስ መረዳዳት እና ለችገሩ መፍትሄ መፈለግ እንጂ መጨቃጨቅ ወይም መጣላት ነገሩን ስለሚያባብሰው ቶሎ መፍትሄ አያገኝም፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ ፅኑ የሆነ የመተሳሰብ ስሜት  እንዲኖር እመክራለሁ፡፡...”  




Published in ላንተና ላንቺ

“እየውልህ የሀገሬ የቀልቁለት ጉዞ መነሻው ኢህአዴግ አይደለም፡፡ ደርግም አይደለም፣ ኃይለስላሴም አይደለም፡፡ ሀገሬ የገባችበት የግለሰባዊ ፣ማኅበራዊና ሀገራዊ ቀውስ አረንቋ መሠረቱ ጥልቅ ነው፡፡--”
      
   ፈራ ተባ እየተባለም ቢሆን የዚች ሀገር ሰቆቃና ችጋር መንስዔ ያ ትውልድ መሆኑን ሲነገር ሰምተናል፤ ሲተች አንብበናል፤ ወይም አብረን ወቅሰናል፡፡ (በዚህ መጣጥፍ ያ ትውልድ ስል የእነ ኢሰፓ፣ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ህወሓት--- የአሁን ዘመን ፓርቲዎች ወዘተ-- የሚያጠቃልል ነው፡፡)
ለምን ያ ትውልድ ተጠያቂ ሆነ? የዚህ መጣጥፍ ዋነኛ ዓላማ አይደለም፡፡ ካነሣነው ዘንድ በጨረፍታ ለመንካት ግን ያ ትውልድ ቂመኝነትን፣ ቁጡነትን፣ ነገር ጠምዛዥነትን፣ ደም መቃባትን፣ ስድብንና  ጥላቻን ሲዘራ የኖረ በመሆኑ ነው፡፡ አሁንም ድረስ በገዥውም ይሁን በተቃውሞ ጎራ ያሉ ፖለቲከኞች ከዚህ አዙሪት አልወጡም፡፡
የአዲሱ ትውልድ አባላት በዚያኛው ትውልድ ሲታመሱና ሲበጠበጡ እስካሁን  አሉ፡፡ የራሳቸውን ማንነት እስኪያጡ ድረስ አለማወቃቸው እየተነገራቸው፣ ሀገር ሊሸከም የሚችል ትከሻና የሚያስችል ጥበብ እንዳልተፈጠረባቸው እየተደሰኮረላቸው፣ ‹‹ድሮ ቀረ›› እየተዜመላቸው፣ ቂምና ጥላቻን እንዴት ማዳበር እንዳለባቸው እየተሰበኩ አሉ፡፡
ለዚህ ይመስላል የሀገሪቱ ፖለቲካ ከ60ዎቹ እስካሁን ድረስ አፍርሶ በመጀመር ቅኝት የተቃኘው፡፡ በእርግጥ ይህም በራሱ ወቀሳ ነው፡፡ ወቀሳ ደግሞ የሰለጠንበት ይሁን እንጅ ትርፋማ ያደረገን ልማድ አይደለም፡፡
በዚህ ስሜት እያለሁ ያነበብኩትን መጽሐፍ መዳሰስ ነው ዋና ፍላጎቴ፡፡ (መጽሐፉን ሶስቴ እንዳነበብኩት ስናገር ግነት አይደለም) ርዕሱ ሽብልቅ፣ ደራሲው ሄኖክ ፍቅረማርያም፣ የገጹ ብዛት 236፣ ዋጋው 50 ብር፣ ዓይነቱ ልብ አንጠልጣይ ልቦለድ፡፡ ከመስመር መስመር፣ ከገጽ ገጽ፣ ከክፍል ክፍል ልብ እያንጠለጠለ የሚጓዝ የአዲስ ትውልድ ምኞት!
በፊት ለፊት ገጹ ላይ ጠመዝማዛና ባላባሎሽ እንጨት ላይ የተሰነቀረ ጉራጅ ብረት ይታያል - ‹‹ሽብልቅ››። በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ደግሞ “ሽብልቅ ማለት ወፍራም ግንድ ለመፍለጥና ለመፈርከስ የምታገለግል ከአናቷ ሰፋ ብላ ወደ ታች እየጠበበች በመሄድ፣ ስለት ያወጣች አጭርና የማትሰበር ብረት ናት›› የሚል ትርጓሜ ተቀምጧል፡፡
ከፊትና ከጀርባ ሽፋን መግለጫዎቹ ተነስተን፣ ከዚህ መጽሐፍ ብዙ መጠበቅ እንችላለን፡፡ ጠመዝማዛውና ወፍራሙ ግንድ ማን ነው? ወፍራምነቱ በራሱ ለመፍለጥ አታካች ነው፤ በዚያ ላይ ባላባሎሽ ያለው ጠመዝማዛ ግንድ…. እንደምን ይፈለጣል? ሽብልቁስ ማን ነው?
አቶ ቢተው የዚህ ሀገር ውጥንቅጥ ያሰለቻቸው የእንስሳት ሀኪም ናቸው፡፡ የህክምና ትምህርታቸውን ተምረው እንደጨረሱ ገጠር ገቡ፡፡ ለሃያ ዓመታት ገጠር ውስጥ ሽብልቅ ሲቆርጡ፣ ሲያቀልጡ፣ ሲቀርጹ ኖሩ፡፡ ይህ ሽብልቅ በእሳት አይደለም የተቆረጠው፣ በግለት አይደለም የቀለጠው፣ በመዶሻ አይደለም የተቀጠቀጠው፤ በእውቀትና በጥበብ እንጂ፡፡  ሽብልቁ ዋለልኝ ነው፡፡
አቶ ቢተው ሚስታቸው ጥላቸው የሄደችው ገጠር ጠላሁ ብላ ነበር፡፡ የከተማ ህይወት አምሯት፡፡ አቶ ቢተው ገጠር የከተሙት ሀገር በቀል ጥበብን ፍለጋ ነው። የሀገሪቱ የፖለቲካ ቅርሻት ለእሳቸው ትርጉም የለውም። የዜጎች ዕለት ከዕለት መኳተን አንድም ለሆድ፣ አንድም ለዝና ስለሆነ ጠልተውታል፡፡ ዘመናዊ እውቀት እየተባለ የሚነገረው ሁሉ ዲቃላ ትውልድን ያፈራ እንደሆነ  እንጂ ሀገር አይቀይርም፤ ለአቶ ቢተው፡፡
ስለዚህም ስር ነቀል ለውጥ፣ አዲስ ለውጥ፣ አዲስ መንገድ ለዚች ሀገር ያስፈልጋታል፡፡ ገጠር ተዳፍነው መሪ ካርታና ፖሊሲ ያዘጋጃሉ፡፡ በዚህ ጥበብ ነው ዋለልኝን የቀረጹት፡፡ ዋለልኝ በቀለም ትምህርቱ እሳት የላሰ ነው፡፡ በሚያኮራ ውጤት አዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲ ይገባል፡፡  አቶ ቢተው ሲሸኙት ይህን ይሉታል፡-
‹‹የኔ ሽብልቅ …. አንተ የምትሄደው ተምረህ ራስህን ለመለወጥ አይደለም፡፡ ተምረህ አባትህን ለመርዳትም አይደለም፡፡ ተምረህ  እናትህን ለመለወጥ ነው…….አዎ ውቧ እናትህ ያለችው እዚህ ነው፡፡ ሉባንጃዋ የሚማርከውና ወዟ የሚፍለቀለቀው ኢትዮጵያ ያለችው እዚህ ነው፡፡ ኩሩና ቆፍጣናዋ እመቤት ያለችው እዚህ ነው፡፡ አንተ የምትሄድበት አዲስ አበባ ያለችው ኢትዮጵያ እብዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ከቆሻሻ ገንዳ ልቅምቃሚ የምትበላዋ.. ጠረኗ የማያስጠጋው… እድፍና ጉድፏ የሚያስጠይፈው ኢትዮጵያ ናት፣ ያዲሳባዋ እናትህ በራሷ የማትተማመን ዝርክርክና ብርክርኳ ኢትዮጵያ ናት እዚያ ያለችው፡፡ ኢትዮጵያ ራሷን የሳተችና ራሷን የማታውቅ ወፈፌ ናት፤ በደም ነፍስ የምትራመድ እግሯ ወደመራት የምትሄድ ወፈፌ፡፡ የፈረንጅ የቆሻሻ ገንዳ ካገኘች እዛው በልታ እዛው የምታድር ማፈሪያና የባዕድ ሀገር መጠቋቆሚያ ናት፡፡
እንዲህ የሆነችው በባህር ማዶ ሰው ነው፡፡ እዚህ የባህር ማዶ ዛፍ እንጂ የባህር ማዶ ሰው የለም፡፡ እንደዚህ ባህር ዛፍ ግዙፍ የሰው ዛፎችና ግንዶች ያሉት አንተ የምትሄድበት አዲሳባ ነው (እነዚህን) ከሃገሬ ለማጥፋት አንተን ሰርቻለሁ፡፡ በእነዚያ እሳት በሚያፈልቁ ደብተሮች ጭንቅላትህን አቅልጬ ሰርቼሀለሁ፡፡ አሁን ያንተ ጭንቅላት ስለት አውጥቷል፡፡  አንተ የኔ ሽብልቅ ነህ (ገጽ-19)
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያገኘሁት ታላቅና አዲስ ሐሳብ፣ ሀገሪቱ መለወጥ ካለባት ስለ ወንበር ፖለቲካና ፖለቲከኞች ማውራት የለብንም የሚል ነው፡፡ በእርግጥ በውዴታና በጥላቻ ጽንፍ ተወጥሮ እዚህና እዚያ ጥላቻን ለሚሰብክ ሁሉ ይህ ሊዋጥ የሚችል ሐሳብ አይደለም። ገዥው ፓርቲ ተቃዋሚዎቼን ሳላጠፋ አልተኛም ይላልና፣ ተቀናቃኞችም ገዥውን ፓርቲ  ድምጥማጡን ሳናጠፋ እንቅልፍ የለንም ይላሉ፡፡ በዚህ መካከል ለሀገር የሚሰጥ ትኩረት እምብዛም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጫጫታ ስለ ምንድን ነው? ስለ እኩልነት? ስለ ፍትህ? ስለ ዴሞክራሲ? እነዚህ ቃላት እኮ ምናባዊ (subjective) ናቸው፡፡ ለምንድን ነው ብርቱ ሀገር ስለ መገንባት፣ መቼም መሠረቷ የማይናወጽ ሀገር ስለመመስረት፣ ገዥዎች ቢቀያየሩ ዕለት ተዕለት አጀንዳዋ የማይለዋወጥ ሀገር ስለ ማነጽ የማይተጉት? ስለዚህስ የማይሰብኩን ለምንድን ነው? ይህ መሠረታዊው የ“ሽብልቅ” መጽሐፍ ማጠንጠኛ ስለሆነ መጽሐፉን ከልቤ ወደድኩት፡፡   
 “እየውልህ የሀገሬ የቀልቁለት ጉዞ መነሻው ኢህአዴግ አይደለም፡፡ ደርግም አይደለም፣ ኃይለስላሴም አይደለም፡፡ ሀገሬ የገባችበት የግለሰባዊ ማኅበራዊና ሀገራዊ ቀውስ አረንቋ መሠረቱ ጥልቅ ነው፡፡ መቼም ሩቅ ነው.--” ስትለው ነዘረው፤ የሆነ ነገር ውርር አደረገው “አንተ ከምሁራኑ ጋር ምን አተካራ አስገባህ? ምሁራን የምትላቸውስ የትኞቹን ነው?››
“በቅድሚያ እንደ ሀገሬ የመኪና ሹፌር እየገጩም እያጋጩም ቢሆን የፖለቲካውን መሪ ጨብጠው የሚያሽከረክሩ በግንባር ቀደምትነት ምሁራን ስለሆኑ ነው፡፡ ምሁራን የምልሽም በቅድሚያ ከፍተኛ የሆነ የሀገር ሀብት እየፈሰሰባችሁ የምትማሩትን እናንተን ሲሆን በመቀጠል የባህልና የሀይማኖት ሊቃውንትንም የሀገርና የመንደር ሽማግሌዎችንም፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የህጻናት መሪ ወላጆችንም ነው” (ገጽ-59)
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ደራሲው መደባበቅና መሸፋፈንን አልፈለገም፡፡ ለማለት ያሰበውን ሁሉ በግልጽ ብሎታል፡፡ የሀሳብ ወጥነት ወይም እንደ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ አባባል “ወርጅናሌነት” አለ፡፡ በዚህ ዳሰሳ ጸሐፊ እይታና የንባብ ደረጃ የማትሽመደመድ ሀገር ለመገንባት አዲስ ቅያስ የቀየሰ ልቦለድ የሄኖክ ፍቅረ ማርያም “ሽብልቅ” ነው፡፡ መንገዱም አዲስ ትውልድ - ‹‹ሽብልቅ›› መፍጠር!
ታዲያ በዚህ ልቦለድ ውስጥ ሐሳባዊነት ብቻ ሳይሆን እውናዊነትም አለ፡፡ አሁን ባለንበት የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሊሆን የሚያስቸግር የሚመስለው አዲስ ትውልድ የማግኘት ራዕይ ሰው በመሆን ሀቅ እየተከሸነ ስለቀረበ ተአማኒነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ከፍ ሲል እንደተባለው ከገጽ ገጽ፣ ከምዕራፍ ምዕራፍ ልብ የመስቀል ሀይሉ ከፍተኛ ነው፡፡ የታሪክ ትውስቡ ምንጭ ደግሞ አሁን ያለው የሁለት ሶስት ትውልድ ባህርይና ስነምግባር ነው፡፡ ልቦለዱ እንደ ሲድኒ ሼልደን ልቦለዶች ጭልጥ ብሎ በምናብ አለም የሚያስዋኝ ወይም እንደ ዳን ብራውን ስራዎች ትርፍ በሌለው የታሪክ ውስብስቦሽ መደመምን የሚፈጥር ብቻ አይደለም፡፡ እየወደድን እናነበዋለን፤ እያተረፍንም፡፡
ያ ትውልድን እንለፈውና እዚህኛው ትውልድ ውስጥ ያለች የያ ትውልድ ቅሪት ይህን ትላለች (ሲመስለኝ ደራሲው ሀቃችንን እየጨለፈልን ነው)
“እክህ ፖለቲካ የሚባል አረንቋ ውስጥ እንዳትገባ አደራህን፡፡ አባቴ ከፖለቲከኝነት ያተረፈው ሲጋራ ይሄውልህ ለእኔም ተርፎኛል፡፡ እኔ ሲጋራ ከመጀመሬ በፊት እሱ የሚያጨሰው ሮዝማን ሽታው እንደ ፓሪስ ሽቶ ይጣፍጠኝ ነበር፡፡ አጫጫሱ ምሁርና አዋቂ አድርጌ እንዳስበው ያደርገኝ ነበር፡፡ እኔም ወደ ዩኒቨርሲቲ ስገባ የምሁርነትና የአዋቂነት አንዱ መስፈርት ማጨስ መስሎኝ ይሄው ተዘፍቄ ቀረሁ፡፡ ፖለቲከኛ ከሆንክ እንደዚህ ሲጋራ የምትነድና የምታነድ ነው የምትሆነው፡፡ የኔ አባት የቅንጅ አባል ነበር፤ ቅንጅት ሲሞት የኔ አባት ራሱን በሲጋራ እያነደደ ነው፤ጋፊዎቹን ደግሞ ሲጋራ ሆኖ እያነደዳቸው ነው›› አለችው፡፡ “……..ተርታው ህዝብ የጤፍ ወይም የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ውስብስቡንና ድብስብሱን ችግር ረስቶ ለዋጋ ግሽበቱና ለእለት ጉርሱ በአንድ ጀምበር መፍትሄን ይሻል፡፡ የዚህ መፍትሄ ደግሞ የወንበር ፖለቲካ ድርጅት ነው ብሎ ማሰቡ የፖለቲካ ነጋዴዎችን የፖለቲካ ድርጅት እንዲያቋቁሙ  እድል ፈጥሮላቸዋል……ድርጅቱ የቆመው የሰራተኛ ደሞዝ እየከፈለ ስራ አጥን ለመቀነስ አይደለምና የቁጥር ቁማር መጫት አለበት። የቁማር ጨዋታው በካርድ ቀጠሮ ወይም ምርጫ ከሆነ ማንኛውንም እኩይና በጎ የጭንቅላት ጨዋታ ሊጫወት ይችላል፡፡ የቁማር ጨዋታው የተበላ እቁብ ከሆነ እቁብ ሁልጊዜ ለአንድ ሰው እንደወጣ ለማሳመን የሥራም የሴራም ጨዋታ ሊጫወት ይችላል……. ነገር ግን የኔ ጉዳይ ህዝባዊ ለውጥ ነው፡፡ ሀገርን ለመለወጥ የወንበር ፖለቲከኛ መሆን ሳይሆን ህዝብን መለወጥ ነው፡፡  ህዝብን ለመለወጥ ከህዝብ ጋር መጣላት ተገቢ የሚሆንበት አጋጣሚም ይሄ ነው” (ገጽ 69-72)
አዎ ሽብልቆች ህዝብ ለመለወጥ ከህዝብ ጋር ይጋጫሉ፡፡ የፓርቲ መቀያየር ሀገር ይለውጣል ብሎ የሚያምን፣ ከአማኝነት ይልቅ ሀይማኖተኝነት ይበጀኛል ብሎ የሚያስብ፣ ከማዕከላዊነት ይልቅ ጽንፈኝነት ይልቃል የሚል፣ ከሀገራዊነት ይልቅ ጎሰኝነት ያዋጣል ብሎ የሚያስብ ሁሉ ከሽብልቆች ጋር ይጋጫል፡፡ ሽብልቆችም ከዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ጋር ይላተማሉ፡፡ የወደድኩት መጽሐፍ! እባክዎ እርስዎም ያንብቡት፡፡  

Published in ጥበብ

ኢትዮጵያ የወይን ጠጅ ጠማቂ ወይም አምራች አገር አልነበረችም፡፡ ስለዚህ ስሟ በወይን ጠማቂ አገሮች ካርታ ላይ አልሰፈረም ነበር፡፡ አሁን ግን በካስቴል የወይን ጠጅ አምራች ፋብሪካ አማካኝነት ከአምና ጀምሮ ስሟ በወይን ጠጅ አምራች አገሮች ካርታ ላይ ሰፍሯል፡፡
በወይን ጠጅ ምርቶቻቸው በፈረንሳይና በሰሜን አፍሪካ ታዋቂ የሆኑት ሚ/ር ካስቴል፤ በኦሮሚያ ክልል በዝዋይ ከተማ ያስገነቡት እጅግ ዘመናዊ የወይን ጠጅ ፋብሪካ ተመርቆ ወደ ገበያ ከገባ እነሆ አንድ ዓመት ሞላው። ፋብሪካው  የተመሠረተበትን የአንደኛ ዓመት የልደት በዓል ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የመጀመሪያውን ዓመት ፌስቲቫል አዘጋጅቶ በፋብሪካው ግቢ አክብሯል፡፡
ከድርጅቱ ጋር የሚሠሩ ወይም ምርቱን ተቀብለው የሚሸጡ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ ደንበኞቻቸው ወይን ጠጁን መሸጥ እንጂ ወይን እንዴት እንደሚጠመቅ አያውቁም፡፡ የወይን ፍሬ ወይም ዘለላ ከየት ተነስቶ የወይን ጠጅ እንደሚሆን የአጠማመቅ ሂደቱን ማሳወቅ የፌስቲቫሉ ዓላማ መሆኑን የካስቴል ፋብሪካ የሽያጭና ማርኬቲንግ ኃላፊ ዓለምፀሐይ በቀለ ገልፀዋል፡፡
ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር 7 ዓይነት የወይን ጠጅ ያመርት ነበር፡፡ አሁን ሁለት ዓይነት ምርት ጨምሮ ቁጥሩን ዘጠኝ አድርሷል፡፡ ደንበኞቻቸው ምርቱን መሸጥ እንጂ አንዱ ከሌላው በምን እንደሚለይ አያውቁም፡፡ ሌላው ዓላማ በዚህ አጋጣሚ ለጠጪና ተቀባይ ደንበኞቻቸው ልዩነቱን ማሳወቅ እንደሆነ ፀሐፊዋ ተናግረዋል፡፡
ወይን፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ ዝርያ ነው፡፡ የተስተካከለ ሙቀትና እርጥበት ካልተደረገለት በቀላሉ ለበሽታ ይጋለጣል፡፡ ፋብሪካው የሚጠቀመውን አራት ዓይነት ዝርያ ቦርዶ ከተባለ የፈረንሳይ ከተማ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው ያመጣው፡፡ “ዘሮቹን ያመጣነው፣ ተስማሚና ምቹ ሙቀትና እርጥበት ባለው ፍሪጅ ነው፡፡ ይህ ጥንቃቄ ብዙ ገንዘብ አስወጥቶናል” ብለዋል -ሃላፊዋ ዓለምፀሐይ፡፡
ወይን ጠጃቸው በመላ ኢትዮጵያ በጣም ተወዶላቸዋል፡፡ ወይን ጠጅ በዓመት ሁለት ጊዜ ማምራት ቢቻልም፣ ካስቴል ግን የሚያመርተው በዓመት አንዴ ብቻ ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው ወይን ብዙ ጊዜ (ኤጂንግ ይባላል) በቆየ ቁጥር የጥራት ደረጃው ስለሚጨምር ነው። አምና ያመረቱት አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ (1.1 ሚሊዮን) ሊትር ወይን ጠጅ በሙሉ ተሸጦ አልቋል። ለአገር ውስጥ ገበያ ካቀረቡት ውስጥ አብዛኛው (80 በመቶ ማለት ይቻላል) የተሸጠው በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ ቀጣዩን ደረጃ የያዘው ደግሞ ደቡብ ክልል መሆኑን ዓለም ፀሐይ ገልፀዋል፡፡
ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ያቀረቡት ምርት በጣም ተወዶላቸዋል። ስለዚህ ማስፋፊያ እየሠሩ ነው፡፡ ካስቴል ወይን ጠጅ ፋብሪካ አ.ማ በሊዝ የወሰደው መሬት 497 ሄክታር ነው፡፡ የመጀመሪያው የወይን እርሻ ያረፈው በ162 ሄክታር መሬት ላይ ሲሆን ከእርሻው 1.1 ሚሊዮን ጠርሙስ ወይን ጠጅ እየተመረተ ነው፡፡ በማስፋፊያው ማምረት የተፈለገው 1.8 ሚሊዮን ጠርሙስ ወይን ስለሆነ 70 ሄክታር መሬት ላይ የወይን እርሻ ሊጨመር ነው፡፡ የቀድሞው እርሻና የፋብሪካ ግንባታ 25 ሚሊዮን ዩሮ ፈጅቷል፡፡ ማስፋፊያው የሚሠራው በ10 ሚሊዮን ዩሮ እንደሆነ ኃላፊዋ ተናግራለች፡፡
ፋብሪካው ወደ ገበያ የገባው አኬሻና ሪፍት ቫሊ የተሰኙ ሰባት ዓይነት የወይን ዝርያ ይዞ ነበር፡፡ አሁን ሁለት ጨምሯል፡፡ ከአኬሻ አራት ዓይነት ወይኖች ይመረታሉ፡፡ አኬሻ ድራይ ሬድ፣ አኬሻ ሚዲየም ሬድ ስዊት፣ አኬሻ ሚዲየም ኃይትና አኬሻ ሚዲየም ስዊት ሮዝ ወይኖች ይመረታሉ፡፡ ድራይ ሬድ ማለት ደረቅ ቀይ ወይን፣ ሚዲየም ሬድ መካከለኛ ጥፍጥና ያለው ቀይ ወይን፣ ሚዲየም ኋይት መካከለኛ ጥፍጥና ያለው ነጭ ወይን ጠጅ ሲሆን፣ ሚዲየም ስዊት ሬድ ሮዝ ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን በኢትዮጵያ የተመረተ ሮዝ ቀለም ያለው ጣፋጭ ወይን ጠጅ ነው። ይህ ወይን ጠጅ የሚመረተው ከቀይ ወይን ሲሆን በፈርሜንተሽን (መብላላት) ሂደት ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀይ ወይን ሳይለወጥ ሮዝ ቀለም ሲይዝ ሂደቱ ስለሚቋረጥ ሮዝ ቀለም ይኖረዋል፡፡ የሚጣፍጠው ደግሞ ስኳር ወይም ሌላ ማጣፈጫ ተጨምሮበት ሳይሆን በፈርመንቴሽን ሂደት የሚፈጠረው ስኳር ሙሉ በሙሉ ወደ አልኮልነት ሳይለወጥ የመብላላት ሂደቱ ስለሚቋረጥ መሆኑን ሃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
ሪፍት ቫሊ ወይን ጠጅም አራት ዓይነት አለው። ሪፍት ቫሊ ካቨርኔሶ ቪኞ ሪፍት ቫሊ መርሎ፣ ሪፍት ቫሊ ሂራ የተባሉት የቀይ ወይን ጠጅ  ዓይነቶች ናቸው፡፡ ካቨርኔሶ ቪኞ ፣ መርሎና ሂራ የወይኑ ዝርያ ስም ነው። ሻዶኔ የሚባለው ወይን ደግሞ ነጭ ቀለም አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት ገበያው የሚፈለገው ነጭ ወይን ስለሆነ ማስፋፊያ የሚደረገው የነጭ ወይን ነው ብለዋል፡፡
ለውጭ ገበያ የሚላኩት ሁለቱም ዓይነት ወይኖች አኬሻና ሪፍትቫሊ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች የሚመርጡት አኬሻን ነው። ምክንያቱ ደግሞ ጠንካራ ስላልሆኑና ስለሚጣፍጥ ነው፡፡ ወደ አሜሪካ፣ አውስትራሊያና ቻይና የሚልኩት ሪፍት ቫሊዎቹን ነው፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ትልቁ ገበያቸው ቻይናና አሜሪካ ነው፡፡ ቀዳሚውን ደረጃ የያዘው ቻይና ነው፡፡ እስካሁን ኤክስፖርት ያደረጉት የምርታቸውን 15 በመቶ እንደሆነ ኃላፊዋ ጠቅሰው፤ ከዚህ በላይ መላክ ቢፈልጉም ቀደም ሲል ኢትዮጵያ በወይን አምራች አገሮች ካርታ ውስጥ ያለመኖሯ ችግር እንደፈጠረባቸው ገልጻለች። ትልቁ ስኬታቸው የአገር ውስጥ ገበያውን ፍላጐት በመቆጣጠራቸው ቀደም ሲል ከደቡብ አፍሪካና ከሌሎች አገሮች ወይን ለማስመጣት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ መቀነሳቸውን አስረድተዋል፡፡
ምርታቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ቢያገኝም ማትረፍ አልቻሉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምርት ከመጀመራቸው ቀደም ሲል የወይን እርሻውን ለአራት ዓመት ሲያለሙ ወጪያቸው በጣም ብዙ ስለነበር ለሁለት ዓመት የሚሠሩት ላለመክሰርና በዋናቸው ለመንቀሳቀስ እንደሆነ፣ ትርፍ የሚጠብቁት በሦስተኛው ዓመት መሆኑን የሽያጭና ማርኬቲንግ ማናጀሯ ገልጻለች።
ወይን የሚጠጣው ምግብ እየተበላ ስለሆነ በፌስቲቫሉ ላይ የተለያዩ አገሮች ከወይን ጋር የሚበሉ ባህላዊ ምግቦች አቅርበው ነበር፡፡ ጆን ሉካ ኢጣሊያዊ ሲሆን የአፍሪካ ወይንና አይብ የሚነግድበት ሬስቶራንት አለው፡፡ ወይን የመጠጣት ልምድ እንዳለው ጠየኩት፡፡ ኢጣሊያዊ ሆኜ እንዴት ነው ወይን የማልጠጣው? አለኝ። እንግዲያውስ ስለካስቴል ወይን ከሌሎች አገሮች ጋር እያነፃፀርክ ስለ ጥራት ደረጃው ንገረኝ ፈለኩት፡፡
አየህ! የወይንን የጥራት ደረጃ የሚወስኑ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ የአየሩ ሞቃት ወይም ቀዝቃዛ መሆን፣ ወይኑ የበቀለበት የአፈር ዓይነት፣ አፈሩ የያዘው ንጥረ ነገሮች ዓይነትና መጠን፣ አካባቢው፣… ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የአፈሩ ዓይነት፣ በተለያዩ አገሮች የሚመረት ወይን ይቅርና በአንድ አገር ውስጥ በተለያየ አካባቢ የሚመረት ወይን እንዟን ማነፃፀር አይቻልም። የካስቴልን ወይን እጠጣለሁ፡፡ ከማንም ጋር ሳይወዳደር በራሱ በጣም ጥሩ ነው አለኝ፡፡  

የአገሪቷን ዘይት ፍላጎት 80 በመቶ ይሸፍናል ተብሏል
             
   ረጲ ሳሙናና ዲተርጀንት አክሲዮን ማኀበር መቀመጫው ሲንጋፖር ከሆነው ዊልማር ኢንተርናሽናል ሊሚትድ ጋር በጋራ ለመሥራት በእኩል (50፣50) ድርሻ ረጲ ዊልማር ማኑፋክቸሪንግ አክሲዮን ማኅበር በ7 ቢሊዮን ብር 14 ማኑፋክቸሪንግ ፋብሪካዎች ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።
የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጡ ሥርዓት የተከናወነው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ረጲ ዊልማር በሁለት ምዕራፍ የማኑፋክቸሪንግ ኮምፕሌክስ ኢንዱስትሪዎችን በሚገነባበት በኦሮሚያ ክልል በሰበታ ከተማ አስተዳደር በዲማ ቀበሌ ሲሆን፣ ይህን ታሪካዊ የሆነ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚ/ር ክቡር ኃይለማርያም ደሳለኝና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ክቡር ሙክታር ከድር ናቸው፡፡
ዊልማር ኢንተርናሽናል ሊሚትድ እ.ኤ.አ በ1991 በማሌዥያ ሲንጋፖር የተመሰረተ ሲሆን፣ የእርሻ ሰብል ምርቶችን በማቀነባበር፣ ደረጃቸው በጠበቁ ዕቃዎች በማሸግና በማከፋፈል በኤስያ  ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅት መሆኑ ታውቋል። ዊልማር ከ50 በላይ በሆኑ አገሮች የንግድ ትስስር ፈጥሮ የሚሰራ ኩባንያ ሲሆን 450 የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችና 95ሺህ ሰራተኞች ያስተዳድራል፡፡
በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰሜን፣ በምዕራብ፣ በደቡብና በምሥራቅ በ13 አገሮች በተለያዩ ዘርፎች የሚንቀሳቀሰው ዊልማር፤ ከ5 ወር በፊት በተጠናቀቀው 2014 ባላውሪክና በፓልም ዘይት ማቀናበር በዓለም ቀዳሚ፣ በኤስያ ግዙፍ የፓልም ዘይት እርሻ ባለቤት፣ በቻይና ግንባር ቀደም የቅባት እህሎችና በአውስትራሊያ ቀዳሚ የስኳር አምራች፣ የፓልም ዘይትና ተረፈ ምርቶች እንዲሁም የሳሙናና ዲተርጀንት ምርቶች ወደ አፍሪካ በማስገባት መሪ ድርጅት መሆኑ በሥነ-ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በመንግሥት ይተዳደር የነበረውን ረጲ ሳሙናና ዲተርጀንት አ.ማን ሊና ኃ.ተ.የግ.ማ በ1999 ዓ.ም ገዝቶ፣ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ያረጁ መሳሪያዎችን በአዲስ መተካታቸውን፣ ከነባሩ ፋብሪካ ተያያዥ የነበረውን 17,306 ካ.ሜ መሬት በሊዝ ገዝተው፣ በውቅር ብረት የማምረቻ መሳሪዎች መትከያ መገንባታቸውንና ፋብሪካው ቀደም ሲል ከሚያመርታቸው የዲተርጀንት ውጤቶች በተጨማሪ በተከሏቸው አዳዲስ መሳሪያዎች የላውንደሪ ሳሙና እያመረቱ መሆኑን የገለጹት የፋብሪካው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ካሚል ሳቢር፣ ሌሎች የምርት ማሳደጊያ ዘዴዎች በመጠቀም፣ 195 የነበረውን የሠራተኛ ቁጥር ወደ 600 በማሳደግ፣ በየዓመቱ የሚያመርተው ምርት የሚያስገኘውን ትርፍ በ10 እጥፍ ማሳደግ መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
አቶ ካሚል አክሲዮን ማኅበሩ፣ ሳሙናና ዲተርጀንት በማምረት ያገኘውን ልምድ በመጠቀም፣ በ600 ሚሊዮን ብር ካፒታል፣ በዓይነቱ አዲስና ዘመናዊ የሆነ የሳሙናና የዲተርጀንት ፋብሪካ ለመገንባት ከሰበታ ከተማ አስተዳደር በፉሪ ቀበሌ 50 ሺህ ካ.ሜ በሊዝ መውሰዳቸውን፤ የሲቪል ግንባታው መጠናቀቁንና የማምረቻ መሳሪያዎቹን ከኢጣሊያ ተገዝተው ሙሉ በሙሉ ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን፣ ለመሳሪያዎቹ ተከላ ዝግጅት እያደረጉ ሳለ ፋብሪካውን የበለጠ ለማዘመንና ምርታቸው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው አብሯቸው የሚሠራ ሸሪክ ኩባንያ ማፈላለግ መጀመራቸው ተናግረዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ መሠረት የካፒታል እጥረት እንዳይፈጠር፣ ዘመናዊ የማኔጅመንት ልምድ ለመቅሰም፣ የተሻለ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም፣ የእውቀት ሽግግር ለማድረግና በቀላሉ ወደ ውጭ ገበያ ለመግባት የውጭ ተባባሪ ኢንቬስተር ሲያፈላልጉ ከሲንጋፖሩ ዊልማር ኢንተርናሽናል ሊሚትድ ጋር ውይይት እንደጀመሩ በተወካያቸው በኩል የገለጹት የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳቢር አርጋው ናቸው፡፡
ዊልማር ኢንተርናሽናል አብሯቸው ሊሠራና በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ በመስማማቱ የስምንት ሰዎች ወጪ ችሎ በማሌዥያና በኢንዶኔዢያ ያሉትን የኢንዱስትሪ ማዕከሎች እንዲጎበኙ እንደጋበዟቸው የጠቀሱት የቦርድ ሰብሳቢው፣ የቴክኒክና የህግ ባለሙያዎችን ይዘው ሄደው ለ15 ቀናት የዘይት፣ የሳሙናና ዲተርጀንት፣ የስንዴ ዱቄት፣ የፓልም እርሻ፣ የግሪስሊንና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች… መጎብኘታቸውንና ዊልማር ኢንተርናሽናል በዓለም አቀፍ ያለውን አቅም፣ የምርቶቹን የጥራት ደረጃ፣ ዘመናዊ አሰራሩን፣ በአጭር ጊዜ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን የመገንባት አቅሙን፣ የወጪና ገቢ ምርቶች ማቀላጠፊያ ዘዴውን፣ የጥሬ ዕቃ፣ የምርት ማከማቻማና ማዘዋወሪያ ሥርዓቱ፣ የምርምር ተቋማቱ፣ የማኔጅመንት አመራሩ የተራቀቀ መሆን እንዳስገረማቸው አቶ ሳቢር አብራርተዋል፡፡
ይህ በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ አቅምና ልምድ ያለው ኩባንያ አብሯቸው ለመስራት በመስማማቱ ረጲ ሳሙናና ዲተርጀንት አ.ማ እና ዊልማር ኢንተርናሽናል ሊሚትድ ኩባንያዎች በእኩል 50 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ፣ በሰበታ ከተማ አስተዳደር በዲማ ቀበሌ በተፈቀደላቸው 100 ሄክታር መሬት ላይ በ7 ቢሊዮን ብር ካፒታል 14 የተለያዩ ፋብሪካዎች ለመገንባት ባለፈው ዓመት ሐምሌ 2006 ዓ.ም በሽርክና (ጆይንት ቨንቸር) አብረው ለመሥራት ውል መፈፀማቸውን  አቶ ሳቢር አርጋው ተናገረዋል። ሁለቱ ኩባንያዎች በገቡት ውል መሠረት የሚገነቡት የፓልም ዘይት ማጣሪያ፣ የሳሙናና ዲተርጀንት፣ የገበታ ቅቤ፣ የሳሙና ሮድልስ፣ ሶዲየም ሲልኬት፣ የላውንደሪ ሳሙና፣ የብሎውና የኢንጄክሽን ሞልድ ፕላስቲክ፣ የዕቃ ማሸጊያ፣ የቅባት ክህሎት ማቀነባበሪያ፣ የግል ንፅህና መጠበቂያ፣ ሱፍና የአኩሪ አተር (ቦሎቄ) የተጣራ ዘይት፣ የስንዴ ዱቄት፣ የማካሮኒና የፓስታ፣ እንዲሁም የማዳበሪያ ፋብሪካዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ረጲ ዊልማር አ.ማ ፋብሪካዎቹን የሚገነባው በሁለት ምዕራፍ ከፍሎ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ካሚል፤ በመጀመሪያው ዙር በ3.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚገነቡት የፓልም ዘይት ማጣሪያ ፋብሪካ፣ የሳሙናና ዲተርጀንት፣ የገበታ ቅቤ፣ የሳሙና ኖድልስ፣ የሶዲየም ሲልኬት፣ የላውንደሪ ሳሙና፣ የብሎውና የኢንጀክሽን ሞልድ ፕላስቲክ፣ የዕቃ ማሸጊያና የቅባት እህሎች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንደሆኑ ገልጸዋል፡
በሁለተኛው ምዕራፍ በ3.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚገነቡት የግል ንፅህና ፋብሪካ፣ የሱፍና የአኩሪ አተር የተጣራ ዘይት፣ የስንዴ ዱቄት፣ የማካሮኒና የፓስታ፣ እንዲሁም የማዳበሪያ ፋብሪካዎች እንደሆኑ ጠቅሰው የመጀመሪያው ዙር ፋብሪካዎች ግንባታ በ18 ወራት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡
አቶ ካሚል ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ የመጀመሪያዎቹ የፋብሪካ ግንባታ ጁን 15 ቀን 2015 ተጀምሮ ቀንና ሌት እየሰሩ በ18 ወራት እንደሚያጠናቅቁ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል። የዘጠኝ ፋብሪካዎች ግንባታ እንዴት በ18 ወራት ያልቃል? ተብለው ሲመልሱ፣ ዊልማርት፣ በኢንዶኔዢያ የ47 ፋብሪካዎች ግንባታ በ3 ዓመት ተኩል መጨረሱን በጉብኝታችን ወቅት አይተናል፡፡ ልምድ ስላለው የዘጠኙን ፋብሪካዎች ግንባታ በ18 ወራት ያጠናቅቃል ብለዋል፡፡
የፓልም ዘይት ማጣሪያ ፋብሪካው ግንባታ እንደተጠናቀቀ ማጣራት ይጀምራል ያሉት አቶ ካሚል፤ ፋብሪካው የሚያጣራው ድፍድፍ ዘይት ከማሌዢያና ከኢንዶኔዢያ እንደሚመጣ፣ ዊልማር 49 መርከቦች ስላሉት አንዱ መርከብ 4,000 ቶን ድፍድፍ ዘይት አምጥቶ በጂቡቲ ወደብ ያራግፋል ብለዋል፡፡ ከጂቡቲ መንግሥት 60 ሺህ ካ.ሜ ቦታ ተረክበው የድፍድፍ ዘይት ማጠራቀሚያ ዴፖ እየገነቡ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ድፍድፍ ዘይቱን በባቡር ወደ ማጣሪያ ፋብሪካው ማመላለሻ 50ሺህ ሊትር የሚይዝ ታንከር እያስገነቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመጀመሪያው ዙር እቅዳችን ከውጭ የሚገባውን ዘይት መተካት ነው ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በዓመት 420 ሺህ ቶን ዘይት እንደሚያመርቱ፣ በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ የዘይት ፍላጎት 530 ሺህ ቶን እንደሚገመትና 420ሺህ ቶን በማቅረብ የገበያውን 80 በመቶ እንደሚሸፍኑ፣ ለገበያ የሚያቀርቡበትን ዋጋ አሁን ላይ ሆነው መናገር እንደማይችሉ ነገር ግን አሁን ከሚሸጥበት ዋጋ እንደሚቀንስ ገልጸዋል፡፡
ሁለተኛው ዙር የፋብሪካዎች ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ የአገር ውስጥ ፍላጎት ካሟሉ በኋላ ምርቶቻቸውን ወደ ጎረቤት አገሮች ማለትም ወደ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ …. በአብዛኛው ለኮሜሳ አባል አገሮች መላክ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህ አገር የሰሊጥ ዘይት ፍላጎት ባይኖርም፣ ቻይናውያን ለምግብ ጣዕም ስለሚፈልጉት እዚህ አምርተን ወደ ቻይና ኤክስፖርት እናደርጋለን፡፡ እዚህም ፍላጎቱ ካለ እናቀርለን ብለዋል፡፡
ከ2 ዓመት በኋላ ወደ ፓልም ተክል እርሻ እንገባለን ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በጋምቤላ አካባቢ እርሻውን ለመጀመር መጠነኛ ጥናት መጀመሩን፣ ዊልማርም እርሻ ለመጀመር የጠየቀ ስለሆነ ከእሱ ጋር በመሆን ጠለቅ ያለ የአዋጪነት ጥናት አድርገን ውጤታማ ከሆነ ወደ እርሻ እንገባለን ብለዋል አቶ ካሚል ሳቢር፡፡
በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ የኢንዱስትሪ ልማት ዋነኛ ሞተር የአገር ውስጥ ባለሀብት እንደሆነ ጠቅሰው አሁን ያሉት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ትንሽ ነው፡፡ አቶ ሳቢር አርጋው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በራሳቸውም ሆነ ከውጭ ኢንቬስተሮች ጋር በመሆን የኢንዱስትሪ ሞተር መሆናቸውን በማሳየታቸው ለእሳቸው ታላቅ ክብርና ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚፈጠሩት ከአገልግሎት፣ ከንግድና ከኮንስትራክሽን ዘርፍ እንደሆነ፣ ለዚህ አብነት አቶ ሳቢርን ጠቅሰው እንደ አቶ ሳቢር ዓይነት ብዙ ሰዎች ስላሉ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በሚያደርጉት ሽግግር፣ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብዋል፡፡
በርካታ ባለሀብቶች በኮንስትራክሽን ዘርፍ መሰማራታቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ባለሀብቶች ብዙ የኮንስትራክሽን ግብአቶች ስለሚጠቀሙ ወደ ኢንዱስትሪ ግብአት ምርቶች ማምረቻ ቢሸጋገሩ በዘርፉ ልምድ ስላላቸው ቀላል ይሆናል፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች ለብቻ ወይም ከውጭ ኢንቬስተር ጋር በመሆን የቴክኖሎጂ፣ የገበያና የእውቀት ሽግግር በማድረግ ለአገር ልማት ሞተር መሆን አለባቸው፡፡ የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ የሚገኘው ከግብርና በመሆኑ የአገራችን ባለሀብቶች ወደ ግብርና ቢገቡ መንግሥት የእርሻ መሬት በማዘጋጀት፣ ብድር በማመቻቸትና አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ድጋፍ በማድረግ ያግዛል ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር ክልሉ ለኢንቬስትመንት አመቺና ምቹ በመሆኑ ወደ ክልሉ ለሚመጡ ኢንቬስተሮች አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር ይደረጋል ብለዋል፡፡
ፋብሪካዎቹ በግንባታ ወቅት ከ6,000 እስከ 8,000፣ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ ደግሞ ከ10,000 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ታውቋል፡፡  

በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ሞተዋል
      አገር ጥለው የተሰደዱ ዜጎች ከ500 ሺህ በላይ ደርሰዋል

    የቀድሞው የብሩንዲ የደህንነት ቢሮ ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል ጎዲፍሮይድ ኒዮምባሬህ ባለፈው ረቡዕ በአገሪቱ መዲና ቡጁምቡራ ከሚገኝ የጦር ካምፕ በሬዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የፕሬዚደንት ኑኩሩንዚዛ አገዛዝ ማክተሙንና አገሪቱን የመምራቱን ሃላፊነት የሚረከብ ጊዜያዊ ብሄራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ያስታወቁ ሲሆን አገሪቱ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ትገኛለች፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከሌሎች አገራት መንግስታት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ወደ ታንዛኒያ መሄዳቸውን ተከትሎ፣ ጄኔራሉ በአገሪቱ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱን ማስታወቃቸውንና በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቡጁምቡራ አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን እንደገለጹ የዘገበው ቢቢሲ፤ አገዛዙን የሚቃወሙ ወታደሮችም በሁለት የጦር ታንኮች ታግዘው ወደ መዲናዋ ማዕከላዊ ክፍል ማምራታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተቃውሞው የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ከትናንት በስቲያም በመንግስት ጦርና በተቃዋሚ ሃይሎች መካከል በቡጁምቡራ ግጭት እንደተከሰተ የጠቆመው ዘገባው፣ ስርዓቱ ይፍረስ የሚለውን የተቃዋሚዎች አቋም በመደገፍ ተቃውሞውን ከተቀላቀሉት የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ጋር በተደረገ ድርድር መፈንቅለ መንግስቱ መቆሙን አንድ የአገሪቱ ጦር መሪ ማስታወቃቸውንም ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ፤ መፈንቅለ መንግስት እንደታወጀባቸው ሲያውቁ ከታንዛኒያ ወደ ብሩንዲ ቢመለሱም፣ ሜጀር ጄኔራል ጎዲፍሮይድ ኒዮምባሬህ አውሮፕላን ማረፊያውና የአገሪቱ ድንበሮች እንዲዘጉ በማዘዛቸው፣ ፕሬዚዳንቱ ወደ አገራቸው መግባት እንዳልቻሉና ወደ ዳሬ ሰላም መመለሳቸውን ያስታወቀው የቢቢሲ ዘገባ፣ ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገጻቸው በኩል ከትናንት በስቲያ ባስተላለፉት መልዕክት የተቃውሞ እንቅስቃሴው በቁጥጥር ስር ውሏል፣ ህገመንግስታዊ ስርአቱም ከአፍራሽ ሃይሎች ተጠብቋል ብለዋል፡፡
የመንግስት ጦር የፕሬዚደንቱን ቤተ መንግስት፣ የብሄራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያውንና አውሮፕላን ማረፊያውን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ ቁልፍ ቦታዎችን እንደተቆጣጠረ ቢያስታውቅም፣ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ግን መዲናዋን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራችን ውስጥ አድርገናል ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
የመፈንቅለ መንግስቱ ቃል አቀባይ ቬኖን ንዳባንዜ በበኩላቸው፤ “መንግስት ተቃውሞውን እንዲገቱ ያሰማራቸው ወታደሮችም ከጎናችን ቆመዋል፣ ድሉ የኛ ነው” ሲሉ ከትናንት በስቲያ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡
ከሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከፖለቲከኞች ጋር በመሆን በአገሪቱ የሽግግር መንግስት መቋቋም የሚችልበትን ሁኔታ እያመቻቹ እንደሚገኙም ሜጀር ጄኔራል ጎዲፍሮይድ ኒዮምባሬህ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኑኩሩንዚዛ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጭ ያለ አግባብ ለሶስተኛ ዙር በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር መዘጋጀታቸውን የተቃወሙ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ከማሰማት ባለፈ፣ አገዛዙን ከስልጣን ለማውረድ መነሳታቸውን የገለጹት ጄኔራሉ፤ ጊዜያዊ ኮሚቴው ብሄራዊ አንድነትን መልሶ በመፍጠርና ምርጫው በፍትሃዊና ሰላማዊ ሁኔታ መካሄድ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት  እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
ከሁለት ሳምንታት በላይ በዘለቀው ተቃውሞ ከ20 በላይ ዜጎች ለሞት መዳረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አገር ጥለው የተሰደዱ ብሩንዲያውያን ዜጎች ቁጥርም ከ500 ሺህ በላይ መድረሱን አመልክቷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ዝንጀሮዎችም እንኳን ከዛፍ ላይ ይወድቃሉ፡፡
የጃፓናውያን አባባል
ሰባት ጊዜ ወድቀህ በስምንተኛው ተነስ፡፡
የጃፓናውያን አባባል
የበሰበሰ እንጨት አይቀረፅም፡፡
የቻይናውያን አባባል
አንዲት ውሸት ሺ እውነቶችን ታጠፋለች፡፡
የጋናውያን አባባል
አመድ መልሶ የሚበተነው ወደበተነው ሰው ፊት ነው፡፡
የናይጄሪያውያን አባባል
ለመብላት የቸኮለ አፉን ይቃጠላል፡፡
የሉሃያ አባባል
ሙቅ ውሃ የሆነ ጊዜ ላይ ቀዝቃዛ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የአይቮሪኮስት አባባል
የልብን ‹ወሬ› ከፈለግህ ፊትን ጠይቀው፡፡
የጊኒያን አባባል
በአፉ አጥንት የያዘ ውሻ መጮህ አይችልም፡፡
የዛምብያውያን አባባል
ሆድ ከፊት ለመሰለፍ አይፈራም፡፡
የናይጄሪያውያን አባባል
የመቃብርን ስቃይ የሚያውቀው የሞተ ሰው ብቻ ነው፡፡
የስዋሂሊ አባባል
አይጥ የቱንም ያህል ብትሰክር ድመት አልጋ ላይ መተኛት የለባትም፡፡
የካሜሩናውያን አባባል
ጨለማውን ከመራገም ሻማ ማብራት ይሻላል፡፡
የቻይናውያን አባባል
ዛፍ በፍሬው ይታወቃል፡፡
የዙሉ አባባል
ትንሽም ኮከብ ብትሆን ጨለማን ትሰብራለች፡፡
የፊንላንዳውያን አባባል
ዕድል ስትጎበኝህ ሁሉም ሰው የምትኖርበትን ያውቀዋል፡፡
የቻይናውያን አባባል
ጥሩ ምክር እንደሚመር መድኀኒት ነው፡፡
የቻይናውያን አባባል



Published in ጥበብ
Page 8 of 19