Saturday, 21 June 2014 14:58

የፍቅር ጥግ

(ስለጋብቻና ፍቺ)
አባት ለልጆቹ ሊያደርግ የሚችለው ትልቁ ነገር፣ እናታቸውን ማፍቀር ነው፡፡
ቴዎዶር ኼስበርግ
ሰዎች በትዳር የሚዘልቁት፣ ስለፈለጉ ነው እንጂ በሮች ስለተቆለፉባቸው አይደለም፡፡
ፖል ኒውማን
ፍቺ አካልን እንደመቆረጥ ነው፡፡ አንዳንዴ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ከተቻለ ግን ባይሆን ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም ዘላቂ አካል ጉዳተኝነትን ያስከትላል፡፡
ቢል ዶኸርቲ
ፍቺ ለልጆች እንዲሁም ለሌሎች ህይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ጤናማ አይደለም፡፡
ዲያኔ ሶሊ
የተሻለ ነገር እስኪመጣ ድረስ ጋብቻን እንደተቋምከእነችግሮቹ  እደግፈዋለሁ፡፡
ዴቪድ ብላንከንሆርን
(የአሜሪካ እሴቶች ተቋም)
እያንዳንዱ ፍቺ የትንሽዬ ስልጣኔ ሞት ነው፡፡
ፓት ኮንሮይ
የህብረተሰብ የመጀመሪያው ማሰሪያ ጋብቻ ነው፡፡
ሲሴሮ
በማህበራዊ ጥናት አንድ አባባል አለ፡- “እናት በመላው ህይወትህ ሁሉ እናት ናት፡፡ አባት ግን አባት የሚሆነው ሚስት ሲኖረው ብቻ ነው”
ሊህ ዋርድ ሲርስ
(የጆርጅያ ጠ/ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ)
ድሮ ወላጆች ብዙ ልጆች ነበራቸው፡፡ አሁን ልጆች ብዙ ወላጆች አሏቸው፡፡
ጉሮ ሃንሰን ሄልስኮግ
አንዳንዴ ባልና ሚስት መጣላታቸው አስፈላጊ ነው፡፡ የበለጠ እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ያደርጋቸዋል፡፡
ገተ
ትክክለኛውን ፍቅር ከመፍጠር ይልቅ ትክክለኛውን አፍቃሪ በመፈለግ ጊዜያችንን እናጠፋለን፡፡
ቶም ሮቢንስ

Published in ጥበብ

        በአጠቃላይ ጥበበኞች ናቸው - የዚያ ሰፈር ልጆች፡፡ ጥበበኞች እና ድሆች:: ድሮም ጥበበኞች ነበሩ ለማለት ግን አይቻልም፡፡ ለአንድ ሰሞን ነው ንሸጣው የሚጠናወታቸው፡፡ ያ ሰሞን ሲያልፍ ወደ ሌላ ተቀይረው ይገኛሉ፡፡ ሁሉንም ነገር መሆን ይችላሉ፤ ንሸጣው ሲጠናወታቸው፡፡ ከዚህ በፊት የፎርጅድ ሰራተኛ ሆነው ነበር፡፡ በተቆረጠ ድንች ማህተም ሲመቱ ይውሉ ነበር፡፡ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፎርጅድ የሀኪም ወረቀት ሲሰሩ ከርመው… የዩኒቨርሲቲ መመረቂያ ወረቀት ለራሳቸው መስራት ሲያቅታቸው ፊልዳቸውን ቀየሩ፡፡ የታክሲ ተራ አስከባሪ እንዳይሆኑ አቅም ያንሳቸዋል፡፡ ሱስና ምናምንቴ አጥቅቷቸዋል፡፡
ከፎርጅዱ በኋላ ተደራጅተው ኮብል ስቶን ለማንጠፍ ሞክረው ነበር፡፡ ከገጠር እንደመጡት ልጆች አቅምም ሆነ አላማ ሲያጥራቸው ወደ ፊልም ፅሁፍ ተሸጋገሩ፡፡ አንድ ላይ ተደራጅተው አንድ ስክሪፕት ፃፉ፡፡ አንድ እስክሪብቶ እየተዋዋሱ፡፡ መሸጡ እንደ መፃፍ ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ ስክሪፕቱን ወደ ቴአትር በመቀየር ላይ እንዳሉ አዲስ ሀሳብ ብልጭ አለላቸው። “ለምን የህልም ጥበበኛ አንሆንም?” ተባባሉ፡፡ ስክሪፕቱንና ትያትሩን ወዲያ ወርውረው የሙሉ ሰአት ህልመኛ ሆኑ፡፡
ገጣሚና ሴተኛ አዳሪ የሚበዛበት የተጨቆነ ሰፈር ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ በከተማው ዙሪያ የተዘረጉት አዳዲሶቹ “ልማታዊ” መንገዶች ወደ እነሱ ሰፈር አቅራቢያ ደርሰው አያውቁም፡፡ በእነሱ ሰፈር ውስጥ ከመኪና የበለጠ የጋማ ከብት ሲዘዋወር ይታያል። የጋማ ከብትና የጋማ ሰው ተስማምቶ ይኖራል፡፡ ከባለሱቆቹ በስተቀር ማንም ቋሚ ገቢ ያለው የለም፡፡
ስለዚህ ህልመኛ መሆን በጣም የሚያዋጣ የስራ ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፈ ብዙ ህልመኛና እብድ በየስርቻው ሲያልጎመጉም ይታያል፡፡ በዚህ ሰፈር ውስጥ ብዙ የፉክክር ፍላጎት የለም፡፡ ፉክክራቸው በተጨባጭ ነገሮች ላይ ሳይሆን በህልም ላይ ብቻ ያጠነጥናል፡፡ ህልም በመፍጠር እና በማባዛት ጊዜያቸውን ይገፋሉ፡፡
አንዱ የጀመረውን ህልም ሌላው ተቀብሎ፣ ቀጥሎበት ያቀብላል፡፡ ህልምን ተውሶ አብሮ ሲተኛት አድሮ ለአበደረው ሰው ይመልሳል፡፡ የኪራይ ክፍያ የለም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ ከሚል ወንጀል ሁሉም ነፃ ናቸው፡፡ በህልሙ የፈጠራትን ሴት ሌላው ጠልፎ ሲያገባ… የተዘረፈው በሰርጉ ላይ ተገኝቶ ያጨበጭባል። አንድ ህልም አግብቶ አብሮ ማርጀት ሞኝነት ነው፡፡ አግባብቷት ይሰነብትና ይፈታታል፡፡ ከህልም ልጅ ማፍራት አይቻልም፡፡
በግጥም ላይ ግጥም ይፈጥራሉ፡፡ በአፋቸው ያወሩታል፡፡ የፈጠሩትን ግጥም ለመፃፍ የሚያበቃ አቅምም ሆነ ምክኒያት የላቸውም፡፡ ህልምን ግጥም ማድረግ ራሱ መግደል እንደሆነ ማመን ጀምረዋል። መፃፍ ግን የማይበሰብስ አፅም መፍጠር ነው፡፡ ማሳተም አፅምን ወደ ሐውልት ቀይሮ እንደ ማምለክ ነው፡፡ ሀጢአት ነው! ህልም ማየት እንዲችሉ ብዙ ነገሮችን ያጨሳሉ፡፡ የሚያጨሱትን ነገር የሚለኩሱት በክብሪት ሳይሆን ከነብሳቸው በተቀጣጠለ እሳት ነው፡፡ ብዙ ነገሮች ይጠጣሉ፡፡ የሚጠጡትን ነገር የሚበርዙት በአምቦ ውሃ ሳይሆን በደማቸው ነው፡፡ የህልም ጥበበኞች ናቸው፡፡
ገፅ እና ባህሪያቸውን መለየት አይቻልም፡፡ ከህልም ሱሰኝነት የተነሳ ገፅታቸው ሁሉ ወደ ቅዠት ተቀይሯል፡፡ ባልተከፈተ በር ወጥተው ይሄዳሉ፡፡ እንደ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ይሾልካሉ፡፡ መናፍስት መሆን እና አለመሆናቸውን እራሳቸውም ለማወቅ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ሰይጣን ሆነው ሳለ የሰይጣን ስም ሲጠራ በርግገው ይንቀጠቀጣሉ፡፡ ህልም ማየት እስከቻሉ ድረስ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መኖራቸው አይገዳቸውም፡፡
ህልም ጎታታ ነው፡፡ ጎታታ ነው ብለው አንቀላፍተው ሲጠብቁት ግን ህልመኛውን ቀድሞት ይጓዛል፡፡ ህልመኛውን ቀድሞ ያደገ የህልም ዝርያ መፈጠሩ በዚያን ሰሞን ሲወራ ነበር አሉ፡፡ ወሬውን ማን እንዳወራው፣ ማን ለወሬው ምክንያት የሆነውን ገድል እንደፈፀመው ግን አይታወቅም፡፡ በህልም የተከናወነ ድርጊትን በእውነተኛው አለም ላይ እንደተከናወነ አድርጎ መተረክም ለዚያ ሰፈር ልጆች ከሀጢያተኝነት ያስፈርጃል፡፡
እናም ይህ ማንነቱ ያልተጠቀሰ ህልመኛ ከፍተኛ ደሀ በነበረበት ጊዜ ያየውን ህልም ነው ጉድ ተብሎ የተወራለት፡፡ አሁን ላይ ይኸ ህልመኛ ከድህነቱም ወጥቷል፡፡ ህልም ማየትንም እርግፍ አድርጎ ትቷል፡፡ ታሪኩ እንደሚከተለው ነው፡-
የእንቅልፍ ቀጠሮ ቢደርስበትም ወደ ፍላጎቱ መድረሻውን መኝታ በማፈላለግ እኩለ ሌሊት ደረሰ። መኝታ ማፈላለግ ብቻም ወደ ግቡ አያደርሰውም። መኝታው ላይ ይዞት የሚያድረው ህልምም ግዴታ ማግኘት አለበት፡፡ ለህልም ስቃይ ማስታገሻ የሚሆን ቁራሽ እንጀራ ለማግኘት በመንደሩ ጉራንጉር እንደ መጥፎ ወሬ ተሽከረከረ፡፡ ቢንከራተትም ህልም የሚያጎርሰው ግን አጣ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ተቀምጦ ለመነ፡፡ ህልምና መኝታ አጥቶ እንዳፈጠጠ አደረ ዋለ፡፡ በዚህ አኳኋን ሳምንታት ዘለቀ፡፡
ከሰው ላይ የተሰረቀ ህልም ይዞ ለመሸጥ ሲሞክር የዋለ የሰፈራቸው ላቦሮ… የሱ ስቃይ በሆነ ተአምር ገብቶት… ወይንም የማይሸጥ ህልም፣ ሸክም ስለሆነበት… ከዚያው ላይ ቀንሶ ሰጠው፡፡ ህልም የተራበው ደሀም ተቀበለው፡፡ ተቀብሎ ጎረሰው፡፡ ጎረሰውና በተቀመጠበት ፍንግል ብሎ ተኛ፡፡
ህልሙ ማስጠንቀቂያ ቢጤ አለው “ያለ ፍቃድ አባዘቶ መሸጥ.. አይቻልም፡፡ እድሜያቸው ከአስራ ስምንት በታች የሆነ ህልመኞች አይመልከቱት…” ወዘተ… ወደ ህልሙ ለመግባት በመቸኮሉ ማስፈራሪያውን ችላ ብሎ አለፈው፡፡ ከማስጠንቀቂያው በኋላ እንደ ማብሪያ እና ማጥፊያ የመሰለ ጉጥ እንደ ሰመመን በተዘጋው አይኑ ውስጥ ተደቀነበት፡፡ ሳይጫነው ቢጠብቅም በደንብ እንቅልፍ አልወስድ ስላለው ፈራ ተባ እያለ ተጫነው፡፡
ህልሙ ጀመረ፡፡ የተዋንያኖቹ ስም ዝርዝር ይወጣል ብሎ አስቦ ነበር፡፡ አልወጣም፡፡ መጀመሪያ የታየው የራሱ ምስል ነው፡፡ “እኔ ተኝቼ እያለምኩ እንዴት ቆሜ ስተውን ታየኝ” ብሎ ግር ሊሰኝ ሲል ነገሩ ተገለፀለት። ተኝቶ በህልሙ ውስጥ እየታየው ያለው ማንነቱ ወደፊት እሱ በምኞቱ ሊሆን የሚፈልገውን ሰው ነው። ደሀው እሱነቱ ተኝቶ፣ ሀብታሙ ምኞቱ ነቅቷል ማለት ነው፡፡
እናም ደሀው ህልመኛ የሀብታሙን ህይወት መመልከት ጀመረ፡፡ ይኼኛው ሜዳ ላይ ተኝቶ እየታዘበ፣ ያኛው ከንጉሳዊ አልጋው ላይ ተነስቶ እያፋሸከ በመንጠራራት ላይ ነው፡፡ አብራው የተኛችው ልጃገረድ ፀጉሯ እንጂ ፊቷ ተከልሏል፡፡ ሃብታምየው ለጥቂት ሰከንዶች ልጃገረዲቷን  በጥሞና ተመለከታት፡፡ አስተያየቱ ላይ ሃዘኔታ፣ መቆርቆርና የአለኝታነት ስሜት ይነበባል፡፡ ደሀው ህልመኛ ሚስቱ መሆን አለባት አለ፡፡ በጨለማ ውስጥ ተቀምጦ ፊልም እንደሚያይ ሰው ነው ትዕይንቱን የሚከታተለው። ተቀምጦ ሳይሆን ተጋድሞ የሚያድርበት ጨለማ ግን ህይወቱ እንደሆነ ይታወቀዋል፡፡ በጨለማው ላይ ፊልሙ ሲያልቅም መብራቱ እንደማይበራ በእንቅልፍ ልቡም ቢሆን አልተጋረደበትም፡፡
ሀብታሙ እሱነቱ ሚስቱን ሲታዘባት ቆይቶ.. እንዳይቀሰቅሳት ተጠንቅቆ ወደ ባኞ ቤት ገባ፡፡ እንደዚህ አይነት ስፋት ያለው ባኞ ቤት እንዳለ ህልም ተመልካቹ አያውቅም ነበር፡፡ የብዙ ሰዎችን የመኖሪያ ሰፈር ያክላል፡፡  ልክ እንደ አልጋው ንጉሳዊ ስፋት አለው፡፡ በሀብታሙ ሰው ህይወት ደሀው ህልመኛ ለምን የክብሪት ሳጥን የሚያክል ጥበት እንደተሰማው አልገባውም፡፡ የዚያኛው ህይወት ከደሀው ህልመኛ ጋር የሚገናኘው በእንቅልፍና ቅዠት ብቻ አለመሆኑ ታወቀው፡፡
ሀብታሙ ፒጃማውን በመስቀያው ላይ ሲያደርግ፣ ደሀው በተኛበት ሆኖ ብርድ አሸማቀቀው። በተጋደመበት መስቀል ላይ የተቸነከረ መሰለው፡፡ ያኛው ሙቅ ሻወሩ ውስጥ ገብቶ በሚሰማው ሙቀት፣ ደሀው እንደ በረዶ ዝናብ እያንዘፈዘፈ ፈጀው፡፡
እንዴት አይቶት የማያውቀውን ነገር ለማለም እንደደፈረ ሊገባው አይችልም፡፡ ከሻወሩ ውሃ የሚወጣውን ሙቀት የሚያጣጥመው ሃብታሙ ነው፤ ደሀው ህልመኛ ከውሃው የሚመነጨውን ደስታ መጋራት አይችልም፡፡ ሀዘኑ ግን ይሰማዋል፡፡ ውሃው ሲፋጅ የሚሰማው ህልመኛውን ነው፡፡ ከዚያኛው ገላ ላይ እየታጠበ የሚነሳው እድፍና ቆሻሻ በተኛው ህልመኛ ላይ ተላከከበት፡፡ ሀብታሙ ከሻወሩ ነቅቶ ሲወጣ ይኼኛው በተኛበት ድካም ይጫጫነዋል፡፡
ሃብታሙ ከሻወሩ ወጥቶ ቲሸርት እና ቁምጣ አድርጐ ከመኝታ ክፍሉ ወጣ፡፡ ኮሪደሩ ላይ ያለውን አንዱን ክፍል ከፍቶ ገባ፡፡ ጂምናዚየሙ የሚገኝበት ክፍል ነው፡፡ ክብደቶቹን ማንሳት ጀመረ። የሚያነሳቸው ክብደቶች እንደ እፉዬ ገላ ቀልለው የሚበንኑ ይመስላሉ፡፡ ፊኛ እንጂ ብረት የሚያንከበክብ አይመስልም፡፡ ተኝቶ ለሚመለከተው ህልመኛ ግን ብረቱ ብረት ሆኖ ሲደፈጥጠው ይሰማዋል፡፡ የሀብታሙ ጡንቻ በእስፖርቱ የሚዳብረውን ያህል የደሀው ህልመኛ ጡንቻ ሲሟሽሽ ይሰማዋል፡፡
ከእስፖርቱ በኋላ ሻወር ለመውሰድ በድጋሚ ባኞ ቤት ገባ፡፡ ታጥቦ ሲወጣ ወደ ተራራ መሳዩ ቁምሳጥን ሄዶ በጥንቃቄ ልብሶቹን መረጠ፡፡ ንፁህ ሱፍ ሰማያዊ ቀለም ያለው፡፡ ከነጮች የነጣ ሸሚዝ፡፡ ክራባቱን አጥብቆ ሲያስር…የተኛው ህልመኛ የመታነቅ ስሜት ተሰማው፡፡ ባለ ክራባቱ በጭካኔ ክራባቱን የበለጠ አጠበቀ፡፡ በጠበቀ ቁጥር የላላ የተፍታታ ንቃት ይሰማዋል፡፡ ደሃውን እያፈነው እንደሆነ የሚያውቅ ይመስላል፡፡ ፈገግታው የጭካኔ ነው፡፡
ደረጃውን ሲወርድ እርምጃው እና ክብደቱ የሚያርፈው በእንቅልፋሙ ደሃ አናት ላይ እንደሆነ የሚያውቅ ይመስላል፡፡ ባለሁለት ፎቅ የሆነውን ደረጃ ወርዶ የተንጣለለው ሳሎን ግርጌ ወደሚገኘው ማዕድ ቤት ገባ፡፡ ሰራተኛው ያሰናዳችው ገበታ ላይ ተሰይሞ ቁርስ ማድረግ ጀመረ፡፡ አጐራረሱ ጤና የተላበሰ ነው፡፡ ህልመኛው በእያንዳንዱ የሀብታሙ ጉርሻ እድሜውን ከሆዱ ውስጥ እየቀነሰበት መሆኑ ተሰማው፡፡ ስቃዩን አልቻለውም፡፡ መንቃት ቢፈልግም ህልምን እንደ ፊልም ጥሎ መውጣት አይቻልም፡፡ በልቶ ሲጨርስ ትልቁን ቦርሳውን በእጁ አንጠልጥሎ ወደ ውሎው ወጣ፡፡ መኪናዋ፤ በማቆሚያ ስፍራ ጭራዋን እንደ ውሻ እየቆላች ጠበቀችው፡፡ ተሳፈራት፡፡ ረገጣት፡፡ ተፈተለከች፡፡
…ቀኑን ሙሉ ከሃብታሙ ጋር በህልሙ ሲንከራተት የዋለው ደሀ …እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰአት ድረስ ነፃ ለመውጣት መቆየት እንዳለበት አልገመተም ነበር። ያኛው ከበላው ክትፎ ያተረፈው የኮሶ ትሉን ነው፡፡ ያኛው ከጠጣው ውስኪ ያተረፈው የጉበት መጠበሱን ነው፡፡ ያኛው ከሚስቱ ጋር ካሳለፋቸው የፍቅር አመታት ደሃው ህልመኛ ያተረፈው በሁለቱም ልብ ውስጥ ያለውን የውሸት ሸክም ነው፡፡ ሁለቱ ከፈፀሙት ወሲብ ያተረፈው ድካሙን ነው፤ ወይንም ጥንቃቄ ከሌለው ወሲባቸው የበሽታ ስጋቱን፡፡
ከአልጋው ትግል በኋላ ሃብታሙ ለመተኛት ብዙ ቢያመነታም እንቅልፍ ጣለው፡፡ እንቅልፍ ሊጥለው ሲል ፈገግ ብሎ በአይኑ ላይ የተደቀነችውን ጉጥ ተጫናት፡፡ እንቅልፍ ወሰደው፡፡ ወፍራም እንቅልፍ፡፡ ጉጧ በሁለት አቅጣጫ የምትሰራ ናት፡፡ ከደሃ ህልመኛ ወደ ሃብታም እርግጠኛ እንደምትወስደው ሁሉ…በተቃራኒው ትሰራለች፡፡ ሀብታሙ ያበራው ተቃራኒውን ነው፡፡ በዛኛው ወፍራም እንቅልፍ ደሃው ነቃ፡፡ ከእነ ድካሙ፤ ከእነ ረሃቡ፣ ከእነ ቁንጫው፣ ከእነ ተስፋ እጦቱ…
የት መሄድ እንዳለበት አያውቅም፡፡ ርቦታል፡፡ በባዶ ሆዱ ሲመለከት ያደረውን ህልም የሰጠውን የተሰረቀ ህልም የሚሸጥ ሰው ለመፈለግ መንከራተት ጀመረ፡፡ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ አዲስ ህልም የሚለውጠው ሰው ካጣ፣ ከዚህ ሃብታም ሰው ጋር በድጋሚ ማታ መፋጠጡ አይቀርም፡፡
የራሱ የህይወት ስቃይ ሳያንሰው የሃብታሙን ደስታ በራሱ ስቃይ እየቀለበ መሆኑ የባሰ አንገበገበው፡፡ ያኛው እንዲኖር ሲባል እሱ እንዲሞት ከህይወት በታች እና ከሞት በላይ ሆኖ እያለመ መቀጠል ይጠበቅበታል።
እሱ የያዘውን ህልም ማንም ስለማይፈልገው የሚለውጠው አጣ፡፡ ቀኑን ሙሉ ህልም ወይንም ራዕይ ሲፈልግ ዋለ፡፡ የባሰ እንጂ የተሻለ አላገኘም፡፡ ሀብታሙ ሲጠጣ እሱ እንደሚሰክረው፣ ደሃው ሲጠጣ ግን ሃብታሙ እንዲያውም ንቁ ሆኖ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ አውቋል፡፡ የሀብታሙን ሸክም ከራሱ ህይወት ላይ ማራገፍ ካልቻለ ቢሞት ይመርጣል፡፡
የሚገጨውን መኪና ቢፈልግም በእነሱ ሰፈር የጋማ ከብት እና ሰው እንጂ መኪና ጠፋ፡፡ ሲመሽ መተኛትን ፈርቶ በእግሩ ሲጓዝ አደረ፡፡ እንቅልፍ አዳፋው፡፡ እንደ ማብሪያና ማጥፊያ የመሰለችው ጉጥ ከፊቱ ተደቀነች፡፡ በእንቅልፍ ልቡ እየተንሰቀሰቀ ተጫናት፡፡
ሃብታሙ ከእንቅልፉ ተነሳ፡፡ ተንጠራራ፡፡ ግን እንዳለፈው ቀን ንቃት አይታይበትም፡፡ ፈዟል፡፡ የተኛችውን ሚስቱንም ዞሮ አላያትም፡፡ ተነስቶ ወደ መስታወቱ አመራ፡፡ የራሱን መልክ አተኩሮ አስተዋለ፡፡ በሆነ ምክንያት ግን እያስተዋለ ያለው የተኛውን እና እሱን በህልሙ በማስተዋል ላይ ያለውን ደሃ ሰው መሆኑ ህልመኛውን ታወቀው፡፡ ለራሱ ጐንበስ ብሎ በመስታወቱ ነፀብራቅ ሰላምታ ሰጠ፡፡ ሰላምታው የአክብሮት ይመስላል፡፡ ተኝቶ የሚያልመው ደሃ …ሀብታሙ የእሱን የደሃ ህይወት ሲታዘብ እንደዋለ ትዝ አለው፡፡ ለምን የእሱን ድህነት እንዳከበረ ሊገባው ግን አልቻለም፡፡ ምናልባት ደሀው ቢሞት ሃብታሙ እያቀለጠ የሚያበራው እና ህይወቱን የሚያስጌጥበት መብራት አይኖረውም፡፡ የመስቀሉ ቋሚ እና አግዳሚ ናቸው፡፡ እጣ ፈንታቸው ከአንድ ጭራ ሁለት መስሎ የተገመደ ነው፡፡ የሃብታምነት ዝቃጮች እና መከራዎች እንደተሸከመው፣ ያኛውም የእሱን የድህነት መስቀሎች በተኛበት ተሸክሞ በማደሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል ያከበረው፡፡
በመስታወቱ ውስጥ ዝቅ ብሎ እጅ ነሳው፡፡ ከእንግዲህ ተሸካክመው መኖራቸው ስለገባው መሆን አለበት፡፡ የአንደኛው ህይወት ከሌላኛው ሞት ጋር መጣመሩ የተቀየረ መሰለ፡፡ ሃብታምየው ገላውን በመታጠብ ፋንታ ዝም ብሎ ልብሱን ለበሰ፡፡ ክራባቱን በማጥበቅ ፋንታ ላላ አደረገለት፡፡ መተሳሰብ አለባቸው፤ ካልሆነ ይጠፋፋሉ፡፡ ደሀ ቀን ቢራብ፣ ሃብታም ማታ… የማታ ማታ መራቡ አይቀርም፡፡
ሃብታሙ በቀን ወደ ደሃው በቀረበ ቁጥር ደሃው በማታ… የማታ ማታ ወደ ሃብታሙ ይቀርባል፡፡ ሃብታሙም ወደ ደሃ ህልም፣ ደሃውም ወደ ተጨባጩ አለም ቀርበው በመሃከለኛ ርቀት መኖር ጀመሩ፡፡ 

Published in ጥበብ
Saturday, 21 June 2014 14:55

ኢራቅ እያበቃላት ይሆን?

        ከዛሬ አስራ አንድ አመት በፊት መጋቢት 20 ቀን 1995 ዓ.ም አሜሪካ የራሷንና የተባባሪዎቿን ሀገራት ጦር አደራጅታ “Shock and awe” (መብረቃዊ አሽመድማጅ ጥቃት) በሚል የሰየመችውን ሁለተኛ ዙር ወታደራዊ የወረራ ዘመቻ በኢራቅ ላይ አካሄደች።
ለዘመቻው መጀመር ያቀረበችው ሰበብ፣ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን ህዝብ ጨራሽ የጦር መሳሪያዎችን በድብቅ እያመረቱ በድብቅ ያከማቻሉ የሚል ሲሆን አንዳንዶች ግን “አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ” የሚለውን ተረት ተርተውባት ነበር፡፡
የሆነ ሆኖ ዘመቻው በተጀመረ ልክ በአስረኛው ቀን፣ መጋቢት 30፣ ወራሪው አሜሪካ መራሽ ጦር፣ ይህ ነው የሚባል የመከላከል ውጊያ ከኢራቅ ወገን ሳይገጥመው ባግዳድን መቆጣጠር ቻለ። በሁለተኛው ወር ግንቦት ሁለት ቀን፣ አሜሪካ በወረራ የያዘቻትን ኢራቅን የሚያስተዳድር ጊዜያዊ የጥምረት ባለስልጣን ማቋቋሟንና ፖል ብሬመር የተባሉት አሜሪካዊ ይህንን ጊዜያዊ የአሜሪካ አገዛዝ በበላይነት እንዲመሩ መሾሟን አስታወቀች፡፡
ፖል ብሬመርም ስራቸውን በይፋ በጀመሩበት ግንቦት 5 ቀን 1995 ዓ.ም ባደረጉት ንግግር፤ “አምባገነኑና ጨቋኙ ሳዳም ሁሴንና የባዝ ፓርቲ አገዛዝ ከመላው የኢራቅ ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግደዋል፡፡ መጪውም የኢራቅ ጊዜ እጅግ ብሩህና ሰላማዊ እንደሚሆን ቅንጣት ታህል እንኳ አያጠራጥርም፡፡” አሉ፡፡ ንግግራቸውን ጨርሰው ቢሯቸው እንደገቡም ከዋሽንግተን አለቆቻቸው የተላኩላቸው ሁለት ዋነኛ ትዕዛዞች ተግባራዊ እንዲሆኑ በፊርማቸው አፀደቁ፡፡ የመጀመሪያው ትዕዛዝ፣ በፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን ይመራ የነበረውና በዋናነት አናሳዎቹ ሱኒዎች ይበዙበታል የሚባለው ገዢው የባዝ ፓርቲ አባላት አዲስ በሚቋቋመው የኢራቅ መንግስት ውስጥ እንዳይካፈሉና ቦታም እንዳይኖራቸው የሚያግድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ትዕዛዝ ደግሞ የኢራቅን የመከላከያ ሰራዊት የሚበትን ነበር፡፡ አሜሪካ በዚህ ብቻ አልረካችም፡፡ በሳዳም ጊዜ “እጅግ ተገፍተናል” የሚሉት ብዙሀን ሺአዎች የጠቅላይ ሚኒስትርነቱንና ሌሎች ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን በመያዝ መንግስቱን እንዲመሩ፣ ኩርዶች ደግሞ ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣን እንዲኖራቸውና ምልክት ብቻ የሆነውን የፕሬዚዳንትነት ቦታ እንዲይዙ በማድረግ፣ አናሳዎቹን ሱኒዎች ከመንግስት አስተዳደሩ ጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ አደረጓቸው፡፡
ይህንን የአሜሪካ ድርጊት የተመለከቱ ታዋቂ የፖለቲካ ተንታኞችና የስነ መንግስት ምሁራን፤ ነገርየው ኢራቅን በቀላሉ ወደማትወጣው የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በማስገባት ህዝቡን ለከፋ የእርስ በርስ እልቂት ይዳርገዋል በማለት፣ አሜሪካ ደግማ ደጋግማ እንድታስብና ከድርጊቷ እንድትቆጠብ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያቸውን አቀረቡ፡፡ ወራሪዋ አሜሪካ ግን “ጆሮ ዳባ ልበስ” ማለትን መረጠች፡፡ “የጠሉት ይወርሳል፣ የፈሩት ይደርሳል” የሚባለው ተረት እውነት ለመሆን አፍታ አልፈጀበትም። አሜሪካ የበተነችውን የኢራቅ የመከላከያ ሰራዊት ይመሩ የነበሩ ሱኒ ጀነራሎችና መኮንኖች የየራሳቸውን ታጣቂ ቡድን በማቋቋም፣ በአሜሪካ ወታደሮችና በመንግስት ሀይሎች ላይ ያልተቋረጠ ጥቃት በማድረስ፣ በሺአይቶች የሚመራውን አዲሱን የኢራቅ መንግስት ቁም ስቅሉን ማሳየት ጀመሩ፡፡
በኢራቅ የሚንቀሳቀሰው የሱኒ ሙስሊሞች የአልቃኢዳ ክንፍም ሺአ ሙስሊሞችን ነጥሎ የጥቃት ኢላማው በማድረግ፣ በጠራራ ፀሐይ የማይቋረጥ ጥቃቱን አፋፋመው፡፡ ሺአ ሙስሊሞች በወጣቱ የሃይማኖት መሪያቸው ሙቅታዳ ሳድር የሚመራ 60 ሺህ አባላት ያሉትና “የማህዲ ሰራዊት” የተሰኘ ታጣቂ የሚሊሻ ቡድን በማቋቋም፣ ለሚሰነዘርባቸው ጥቃት አፀፋውን ለመመለስ ቢሞክሩም የረባ ውጤት ማግኘትና የሱኒዎችን ጥቃት ማስቆም አልቻሉም፡፡ በዚህ የእርስ በርስ ፍጅት የተነሳም ኢራቅ በአማካይ 30 ዜጐቿን በየቀኑ ለመቅበር ተገደደች፡፡
በሳዳም ሁሴን የባዝ ፓርቲ የአገዛዝ ዘመን የነበራቸውን የበላይነት ያጡትና በሺአዎች ቁጥጥር ስር ባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ኑሪ አልማሊኪ መንግስት ከጨዋታ ውጪ የተገፉት ከኢራቅ ጠቅላላ የህዝብ ብዛት 35 በመቶ የሚሆኑት አናሳዎቹ የሱኒ ሙስሊሞች፤ በተለይ የአሜሪካ ወራሪ ወታደሮች ኢራቅን ለቀው ከወጡበት ከ2003 ዓ.ም በኋላ የኢራቅ መንግስት ላይ የሚወስዱትን የጥቃት እርምጃ አባብሰው ቀጠሉበት፡፡
እነዚህ ሃይሎች ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ግን “Islamic State in Iraq and the Levant” ወይም ISIL በሚል ምህፃረ ቃል (Levant የሚለው ቃል ከኢራቅ በተጨማሪ ሶርያን፣ ሊባኖስን፣ እስራኤልን፣ ዮርዳኖስን፣ ቆጵፕሮስንና ደቡባዊ ቱርክን የሚያጠቃልለውን ክልል ያመለክታል) የሚጠራ በወጉ የተደራጀ፣ የታጠቀና አዲስ ልዩ ሃይል በማቋቋም በመንግስት ሀይሎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከፍተዋል፡፡
ጥቃቱን መቋቋም ያቃተው የመንግስት ሃይልም የታጠቀውን መሳሪያ እየጣለ እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ከመፈርጠጥ የሚያቆመው አልተገኘም፡፡ 30 ሺ የሚሆኑት የመንግስት ሃይሎች የኢራቅ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ የሆነችውን ሞሱልን ለቀው እግሬ አውጭኝ ያሉት የመንግስት ወታደሮች ስምንት ሺ የሚሆኑትን የአይሲስ ታጣቂ ሃይሎችን ለግማሽ ሰዓት ያህል እንኳን መዋጋት አቅቷቸው ሸሽተዋል ተብሏል፡፡ አይሲስ አሁን ባግዳድን ለመቆጣጠር በሠላሳ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
የቡድኑ እንቅስቃሴ በኢራቅ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ሀገራት ላይም ጥቁር ጥላውን አጥልቷል። ሀይማኖትና ብሔራዊ ጥቅም ኢራንን፣ ሶርያን፣ አሜሪካንንና ተባባሪዎቿን ለጣልቃ ገብነት ጋብዟል፡፡ ሁኔታውን በቅርብ የሚያውቁ ተንታኞችና ምሁራን፤ ኢራቃውያን ከእርስበርስ እልቂት የሚታደጋቸው ሃይል ቢያገኙ እንኳ ሀገራቸው መቼም ቢሆን የበፊቷን ኢራቅ እንደማትሆን ተንብየዋል፡፡ የምር ግን ኢራቅ እያበቃላት ይሆን?

Published in ከአለም ዙሪያ

    ያልተቋረጠ የሽብር ጥቃት ከራሳቸው ላይ አልወርድ ብሎ እጅግ ግራ የተጋቡ ሁለት የአፍሪካ ሀገራት አሉ ከተባለ ከኬንያና ናይጀሪያ ውጭ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ያላባራ የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆነችው ኬንያ፤ ባለፈው እሁድና ሰኞ በተከታታይ የወረደባት የሽብር መአት የጦርነት ቀጠና አስመስሏታል፡፡
የአልሸባብ አባላት ሳይሆኑ እንዳልቀረ በሰፊው የተጠረጠሩ ሽብርተኛ ታጣቂዎች ባለፈው እሁድ የሱማሊያ አዋሳኝ የኬንያ ግዛት ከሆነችው የላሙ ደሴት አቅራቢያ በምትገኘው የምፒኪቶኒ ከተማ ላይ ድንገት አደጋ ጥለው አርባ ስምንት ኬንያውያንን ገድለዋል፡፡ እሁድ እለት ማታ ላይ ከተፈፀመው ከዚህ ጥቃት ያመለጡ የአይን እማኞች፤ ሽብርተኛ ታጣቂዎቹ ቤት ለቤት እየዞሩ የቤቱ አባወራ ሙስሊም መሆኑንና የሶማሊያ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን አለመሆኑን ያጣሩ እንደነበረ ጠቁመው በተለይ ሆቴል ውስጥ ካገኟቸው ወንዶች ውስጥ ሙስሊም ያልሆኑትን ብቻ ለይተው በማውጣት፣ሚስቶቻቸው ፊት በጥይት ደብድበው እንደገደሏቸው አስረድተዋል፡፡
የምፒኪቶኒ ከተማ ነዋሪም ሆነ መላ ኬንያውያን የዚህ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ድንጋጤ ገና በወጉ እንኳ ሳይለቃቸው ሰኞ እለት ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የማጂምቤኒ ከተማ እነዚሁ ሽብርተኛ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የአስር ኬንያውያንን ህይወት ቀጥፈዋል፡፡
ድፍን አለሙም ሆነ መላ ኬንያውያን እንደጠረጠሩት፣ የሶማልያው ሽብርተኛ ቡድን አልሸባብ ኬንያ በሶማልያ ላይ ለፈፀመችው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትና በሙስሊሞች ላይ ላደረሰችው በደል ሁለቱንም ጥቃቶች በማድረስ የእጇን እንደሰጣት በመግለፅ ሃላፊነቱን ወስዷል፡፡
የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ግን አልሸባብ የሰጠው መግለጫ ፈጽሞ ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡ በሽብር ጥቃቱ ከተገደሉት አብዛኞቹ የእሳቸው ብሔር አባላት የሆኑ ኪኩዩዎች መሆናቸውን መሰረት በማድረግ ሃላፊነቱን ከወሰደው አልሸባብ ይልቅ በዘረኝነት የታወሩ ባሏቸው ኬንያውያን ፖለቲከኞች ላይ ጣታቸውን በመቀሰር ተጠያቂ አድርገዋቸዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱን ውንጀላ ተከትሎም የኬንያ ፖሊስ በሽብር ጥቃቱ እጃቸውን አስገብተዋል ያላቸውን በርካታ ኬንያውያንን ከያሉበት ለቃቅሞ ወህኒ ከርችሟቸዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Saturday, 21 June 2014 14:51

የብራ መብረቅ በናይጀሪያ

ቦኮ ሃራም ባጠመደው ቦንብ 21 ወጣቶች ሲሞቱ፤ 27ቱ ቆስለዋል

ናይጀሪያውያን የእኛን ቡድን በደርሶ መልስ ጨዋታ አሸንፎ ለ20ኛው የአለም ዋንጨ ባለፈው የአፍሪካ ሻምፒዮን ብሔራዊ ቡድናቸው በእጅጉ ደስተኞች በመሆናቸው የብራዚሉ የአለም ዋንጫ እስኪጀመር በጣም ቸኩለው ነበር፡፡
አብዛኞቹ ናይጀሪያውንም ቡድናቐው ተካፋይ የሆነበት የብራዚሉ የአለም ዋንጫ,ኧ እስከ ፍፃሜው ድረስ (ያለው የአንድ ወር ጊዜ በየአደባባዩ ተሰብስበው የሚዝናኑበት አሪፍ የፌሽታ ጊዜ እንደሚሆንላቸው ሙሉ እምነት ነበራቸው፡፡
የሰሜን ምስራቅ ግዛቶች ውስጥ በሚኖሩት ናይጀሪያውያን ዘንድ ግን ይህን መሰሉ ስሜት ብዙም አልቆየም፡፡ ፅንፈኛ እስላማዊ አሸባሪ ቡድን የሆነው ቦኮ ሃራም በዋናነት ይንቀሳቀስበታል በሚባለው በዚህ አካባቢ የዓለም ዋንጫን መመልከት የታገደው ከጨዋታው ቀደም ብሎ ነው፡፡ ቦኮ ሀራም በዮቤና በአዳማዊ ግዛቶች “አዳሜ ሁሉ የአለም ዋንጫ ውድድርን በአደባባይ ተሰብስቤ እየጨፈርኩ በቴሌቪዥን እከታተላለሁ ስትል ውርድ ከራሴ!” በማለት በበራሪ ወረቀት የሰጠው ማስጠንቀቂያ ብዙዎችን ከፍ ያለ ስጋት ውስጥ መጣሉ አልቀረም፡፡
በእግር ኳስ ፍቅር ልባቸው ክፉኛ የነደደ በርካታ ናይጀሪያውያን ግን ስጋታቸውን እንደያዙም ቢሆን ሰብሰብ ብለው እየጨፈሩ ውድድሩን ከመመልከት ወደኋላ አላሉም፡፡ የዮቤ ግዛት የዳማቱሩ ከተማ ነዋሪ የሆኑ እግር ኳስ አፍቃሪ ናይጀሪያውያን ባለፈው ማክሰኞ ያደረጉትም ይህንኑ ነበር፡፡
ለቦኮ ሀራም ግን የእነዚህ ናይጀሪያውያን ድርጊት ማስጠንቀቂያን ቸል የማለት ተራ ስህተት ሳይሆን በሞት የሚያስቀጣ ከፍተኛ ወንጀል ነበር፡፡ እናም የቅጣት ቦምብ ተጠመደላቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት ብራዚልና ሜክሲኮ እየተጫወቱ ሳለ ማንም ባላሰበውና ባልጠበቀው ሁኔታ የተጠመደው ቦምብ ድንገት ፈነዳ፡፡ አገር ሰላም ብለው ጨዋታውን በመከተተል ላይ ከነበሩት ወጣቶች መካከል ሃያ አንዱ ወዲያውኑ ሲሞቱ፤ ሃያ ሰባቱ የሚሆኑት ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ብዙዎችን ድንጋጤ ውስጥ የከተተ የብራ መብረቅ!

Published in ከአለም ዙሪያ

ሊሲና አፈጻጸም ካልተጣጣመ ከባድ አደጋ ይፈጥራል - የእስራኤል የቢዝነስ ልዑካን ቡድን አባል
ቢሮክራሲ የሰለቸው ኢንቨስተር አማራጩ ጥሎ መሄድ ነው
            በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሚ/ር አቪጋዶር ሊበርማን የተመራ 50 አባላት ያሉት  የቢዝነስ ልዑካን ቡድን ሰሞኑን ከኢትዮጵያ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ የልዑካን ቡድኑ፤ ከእርሻና ውሃ ቴክኖሎጂ፣ ከኢነርጂና ማዕድን፣ ከሕይወታዊ ሳይንስ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከማዕድን ቁፋሮና ከመሰረተ ልማት ኢንዱስትሪ፣ ከባንክ፣ ከአገር ደህንነት (ሆምላንድ ሴኩሪቲ)፣ ከአማካሪና ከአቪዬሽን፣ … ዘርፎች የተውጣጣ ነው፡፡
ቡድኑ ጉብኝት ያደረገው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአራት የአፍሪካ አገራት:- በሩዋንዳ፣ በኮትዲቯር፣ በኬንያና በጋና ጭምር ነው፡፡ የእስራኤላውያን የቢዝነስ ሰዎች የአፍሪካ ጉብኝት፣ ትልቅ ዓላማ እንዳለው ከልዑካን ቡድኑ ጋር የመጡት ትወልደ ኢትዮጵያዊው ቤተ እስራኤላዊ ኢንቨስተር አቶ ለማ ልጅኢሻል ይናገራሉ፡፡
አቶ ለማ እስራኤል የገቡት ከ24 ዓመት በፊት ነው፤ በ1982 ዓ.ም፡፡ በመንግሥትና በግል ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት አቶ ለማ፤ ቀደም ሲል የሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች አማካሪ ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀዳሚ በሆነውና አሽግድ በተባለው የእስራኤል ወደብ እየሰሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩት ጊዜ፣ ወላጆቻቸው በሁመራ የሰሊጥ እርሻ ነበራቸው፡፡ እሳቸውም ከዘጠኝ አመት በፊት (ከ2009 ጀምሮ) ኢትዮጵያ መጥተው በሁመራ ሰሊጥ እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሰሊጥ አምራች ብቻ ሳይሆኑ ኤክስፖርትም ያደርጋሉ፡፡ በየዓመቱ ከ100 እስከ 150 ኮንቴይነር ሰሊጥ፣ ሽምብራ፣ ጤፍ፣ የቅባት እህሎች ኤክስፖርት ያደርጋሉ፡፡ በሁለትና ሦስት ወር ስለሚመጡና ወኪሎችም ስላላቸው፣ ቢዝነሳቸው ጥሩ እየሄደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አቶ ለማ፣ የእስራኤል የቢዝነስ ሰዎች፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲና የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲና የቢዝነስ አማራጭ ባደረጉላቸው ገለጻ፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት የአንድ ለአንድ የልምድ ልውውጥና የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረገላቸው አቀባበል ከልብ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት፣ ከ5 እና 6 ዓመት ወዲህ የሚከተለው የኢንቨስትመንት ፖሊስ፣ ለልማት አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል፤ እኛም የምንመላለሰውና የውጭ ኩባንያዎችን እያሳመንን የምናመጣው መንግሥት ለውጭ ዜጎችና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ያዘጋጀው የኢንቨስትመንት ሕግ አመቺና አደፋፋሪ ስለሆነ ነው፡፡ አገራችን ደግሞ ለልማት ምቹ ናት፡፡ መንግሥት፤ ለሚሊኒየሙ የመጣን ጊዜ፣ ከዚያም ወዲህ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ እየተዘዋወረ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣ የቢዝነስ አመቺነትና አማራጮች፣ … ለውጭ ዜጎችና ለዲያስፖራው የሚያደርገው ገለጻ በጣም ጥሩ ከመሆኑም በላይ ለኢንቨስትመንት ቆርጦ መነሳቱን ያመለክታል ብለዋል፡፡
የእስራኤል ትላልቅ የቢዝነስ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ይላሉ - አቶ ለማ፡፡
ከ6 ዓመት በፊት በውጭ ጉዳይ የተመራ ቡድን መጥቶ ነበር፡፡ ከሦስት ወር በፊትም እኔም ያለሁበት 50 የቢዝነስ ልዑካን መጥተን ነበር፡፡ የአሁኑ ቡድን ጉብኝት በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም - በአፍሪካም ነው። ከሩዋንዳ፣ ከኮትዲቯርና ከጋና ጉብኝት በኋላ ነው ኢትዮጵያ የመጣነው፡፡ በኬንያ በምናደርገው ጉብኝት ነው የምናበቃው፡፡
እስራኤል ቴክኖሎጂና እውቀት እንጂ ለኢንቨስትመንት የሚሆን የተፈጥሮ ሀብት የሉትም። የነበራትንም ስለጨረሰች እውቀትና ቴክኖሎጂዋን ኢንቨስት የምታደርግበት ትፈልጋለች፡፡ ለዚህ ደግሞ አፍሪካ ተመራጭ ነች፡፡ “በአፍሪካ ኢንቨስት ማድረግ ተረስቶ የቆየ ጉዳይ ነው” ብላ ስላመነች ነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን ይዛ የቢዝነስ አማራጭ አገር የምታስሰው፡፡ ስለዚህ ቡድኑ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል፡፡  
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ያለውን ችግርም አልደበቁም፡፡ አንድ ችግር አለ፡፡ ከመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከዓለም ባንክና ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር በተወያየንበት ወቅት ተናግሬዋለሁ፡፡ የኢንቨስትመንት ፖሊሲውና መንግስት ለቢዝነስ ያለው አመለካከት ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ቢሮክራሲው ከባድ ማነቆ ነው። ከላይ የሚነገረውና እታች የሚፈጸመው አይገናኙም። ታች በዞንና በወረዳ ያሉት አመራሮች ኢንቨስተሩን አልተረዱትም፡፡ ሊያለማ ሳይሆን የሚበላው አጥቶ እርቦትና ቸግሮት የመጣ ነው የሚመስላቸው፡፡ በብሔራዊ ደረጃ ያለው ፖሊሲ ሌላ፣ አፈጻጸም ሌላ። የፌዴራል ፖሊሲና የክልል አፈጻጸም ካልተቀናጀ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ የፖሊሲ ማማር ብቻውን ምንም አይሰራም፡፡ እታች ብዙ ችግር አይቻለሁ፡፡ አመራሮቹ አብረሃቸው እንድትበላ እንድትጠጣ፤… ይፈልጋሉ፡፡ ኢንቨስተሩ ደግሞ ጠቅሞ ለመጠቀም እንጂ ለዚህ ዓይነት አሰራር ቦታ የለውም - ጥሎ ነው የሚሄደው፡፡
ብዙ ጥሬና አሳምኜ ያመጣሁት አንድ ኢንቨስተር፣ ሥራ ጀምሮ ነበር፡፡ 10 ዓመት ከሥራ በኋላ የታች አመራሮች “የሊዝ ክፈል” አሉት፡፡ “ለ40 ዓመት ነው’ኮ የተዋዋልነው” ቢልም ሰሚ አላገኘም፡፡ ለክልል ጽ/ቤት አመለከተ፡፡ ውላቸው እንደዚያ ባይሆንም ክልልም፣ የበታች አመራሮችን ሐሳብ ደግፎ “ከ10 ዓመት በኋላ የሊዝ መክፈል አለብህ” በማለት ወሰነ፡፡ ኢንቨስተሩ፣ እምነት በሌለበት በዚህ አይነት መንገድ መቀጠል ስላልፈለገ ጥሎ ወደ ሌላ ክልል ሄደ፡፡
ቢሮክራሲው በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ መልኩን ለውጦ ይመጣል፡፡ የዚህ ዓይነት ቢሮክራሲ የሰለቸው ኢንቨስተር የሚወስደው እርምጃ ተመሳሳይ ነው - ጥሎ መሄድ፡፡ የበለጠ የሚጎዳው ክልሉ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአሰራር እውቀት፣ …. ያመጣ፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል የፈጠረ ኢንቨስተር ጥሎ ሲሄድ፣ ጉዳቱ የሚያመዝነው ማን ላይ እንደሚሆን መገመት አያቅትም፡፡ እዚህ ላይ ነው መንግሥት ጠንክሮ መሥራት ያለበት፡፡ ፖሊሲውና አፈጻጸም ካልተቀናጀ አገሪቷ ከባድ አደጋ ውስጥ ናት ማለት ነው፡፡
ሌላ የምለው ነገር መንግስት ለኤክስፖርት ምርቶች ትኩረት ሰጥቶ ምርታቸው እንዲጨምር ማድረግ አለበት። ምርት ባነሰ ቁጥር ዋጋ መጨመሩ ከሌላው አገር ጋር ለመወዳደር ከባድ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ጥራቱ ጥሩ ቢሆንም ምርቱ አነስተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ምርቱ ዝቅተኛ በሆነ መሬት ላይ ማዳበሪያ በመጠቀም፣ ምርቱን ማሳደግ ያስፈልጋል በማለት አቶ ለማ ልጅኢሻል ለአገሪቷ ይበጃል ያሉትን ምክር ሰጥተዋል፡፡
አቶ ደረጀ ዳርጌ በኮንስትራክሽንና በማማከር ዘርፍ የተሰማራ ኢንቨስተር ነው፡፡ ከእስራኤል ከመጡ ኩባንያዎች ጋር በጋራ ሊሰሩ በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል፡፡ የተያዘለት ፕሮግራም ከ3 ድርጅቶች ጋር የልምድ መለዋወጥ ቢሆንም አንዱ አልመጣም፡፡ ከሁለቱ ጋር ግን ተወያይቶ ጥሩ መግባባትና የልምድ ልውውጥ እንዳደረገና ወደፊት የበለጠ ለመቀራረብ አድራሻ መለዋወጡን ገልጿል፡፡
ከእኔ ጋር ውይይት ያደረጉት ድርጅቶች ሥራ የጀመሩና ለመጀመር በዝግጅት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ጥሩ የልምድ ልውውጥ አድርገናል፡፡ ሁለታችንም የምንፈልገው ነገር አለ፡፡ እኛ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማኔጅመንት እውቀት እንፈልጋለን፡፡ እነሱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ቢዝነስ መስራት እንደሚቻል ስለማያውቁ፣ ልምድ ተለዋውጠን በጋራ መጠቀም የምንችልበትን መንገድ ለማመቻቸት ተግባብተናል ብሏል፡፡
አቶ ተፈሪ አስፋው በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ልዩ አማካሪ ናቸው፡፡ ስብሰባው ውስጥ አገኘኋቸውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከብዙ አገራት የቢዝነስ ሰዎች በቡድን እየመጡ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ለመሆኑ ፍላጎት ብቻ ነው? ወይስ ኢንቨስትም ያደርጋሉ? አልኳቸው፡፡
አሁን ቁጥሩን በትክክል ልነግርህ አልችልም እንጂ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ብዙ ኢንቨስት ያደረጉ ኩባንያዎች አሉ፡፡ የንግድ ም/ቤቱ ዓላማ የአገር ውስጥና የውጪዎቹን የንግድ ማኅበረሰብ በማቀራረብ፣ የውጪዎቹ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማግባባት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት ከኔዘርላንድስ፣ ከሕንድ፣ ከቱርክ፣… በም/ቤቱ አስተባባሪነት የመጡ ባለሀብቶች በአገራችን ኢንቨስት በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። መንግሥትም የኢንቨስትመንቱን አዋጅ በማሻሻሉ በዚያ እየተሳቡ የመጡ ኢንቨስተሮችም አሉ፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ከአሜሪካ ከእንግሊዝ፣ … የመጡም አሉ፡፡ በ
ቅርቡ የኦባማ የኢነርጂ ኢኒሸቲቭ ኮንፈረንስ በአገራችን ተካሂዶ ነበር። በዚያ ጉባኤ ለመሳተፍ የመጡ የአሜሪካና የሌሎች አገራት ባለሀብቶች፣ በግላቸው ወይም ከኢትዮጵያውያን ጋር በሽርክና ኢንቨስት ለማድረግ ተስማምተዋል በማለት ገልጸዋል፡፡  

ኮንሶ ወረዳ ከሶስት አመታት ወዲህ በበርካታ ቱሪስቶች አይን ውስጥ እየገባች መጥታለች፡፡
ቱሪስቶቹ ግን የተሟላ ማረፊያና አገልግሎት ቢፈልጉም ካራት ከተማ ገና በእንቅስቃሴ ላይ በመሆኗ የእንግዶቿን ፍላጐት ለማሟላት እየተፍጨረጨረች ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከከተማዋ አናት ላይ በሚገኘው ከፍተኛ ቦታ ላይ የተንጣለለው “ካንታ ሎጅ” ከተከፈተ በኋላ በመጠኑም ቢሆን ቱሪስቶች ደረጃውን የጠበቀ ማረፍያ ማግኘት ችለዋል፡፡ ምንም እንኳን በቂ ባይሆንም፡፡ በአካባቢው ስለሎጁ አመሰራረት፣ የስራ እንቅስቃሴና ስለሚሰጠው አገልግሎት ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከሎጁ ስራ አስኪያጅ ከአቶ አሰፋ ቢርቦ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡


ሎጁ መቼ ነው አገልግሎት መስጠት የጀመረው?
ግንባታው ረዘም ያለ ጊዜ ወስዷል፡፡ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ግን ከሶስት ዓመት በፊት ነው፡፡
የሎጁ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
የገበያው ሁኔታ እንደወቅቱ ይለያያል፡፡ ሃይ ሲዝን እና ሎው ሲዝን የሚባል አለ፡፡ እንደወቅቱ ይለያያል። በእርግጥ አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኑ በርካታ ቱሪስቶች ወደከተማዋ ሲመጡ የተሻለ አገልግሎት የሚያገኙበት ሎጅ ነው፡፡ እኛም የምንገኘው አማካኝ መንገድ ላይ በመሆኑ እንቅስቃሴው ጥሩ ነው፡፡
ባሩ፣ ሬስቶራንቱም ሆነ የመኝታ ክፍሎቹ የውስጥ አደረጃጀታቸው ዘመናዊ ሆኖ ከውጭ ግን ባህላዊ ነገሮችን ተጠቅማችኋል፡፡ የሎጁ አሰራር የኮንሶን ባህል ይወክላል ብለው ያስባሉ?
በደንብ ይወክላል! መጀመሪያውኑም የኮንሶን ባህላዊ ገጽታዎች በሙሉ እንዲያንፀባርቅ ተደርጐ ነው የተሰራው፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የኮንሶን ማህበረሰብ የሚጠቀምባቸው ወንበሮች፣ መጋረጃዎች፣ ጣሪያውም ግድግዳውም ይመሳሰላል፡፡ ነገር ግን ሌሎች ዘመናዊ ነገሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ዘመናዊ ነገሮችንም ተጠቅመናል፡፡ ይህን ያደረግነው ለእንግዶቻችን የበለጠ ምቾት ለመጨመር ነው፡፡ ቦታው ቀደም ሲል ሎጁ ከመገንባቱ በፊት በጣም ገደላማ ስለነበር፣ ከኮንሶ ታታሪ ህዝብ የተማርነውን የእርከን አሰራር በመጠቀም፣ ቦታውን ለሎጁ ግንባታ አመቺ እንዲሆን አድርገነዋል፡፡
ከሌላው ለየት ያለ አገልግሎት እንደምትሰጡ ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለምትሰጧቸው አገልግሎቶች ትንሽ ያብራሩልኝ?
እንደማንኛውም ሎጅ የመኝታ፣ የባርና የምግብ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ የተለየን የሚያደርገን የምንሰጠው አገልግሎት ጥራትን ማዕከል ያደረገና ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ነው፡፡ ሎጁ በትልልቅ ከተሞች የሚገኝን ትልቅ ሎጁ ይመጥናል፡፡ በማደግ ላይ ላለችው ካራት ከተማ፣ ትልቅ ግርማ ሞገስ አጎናፅፏታል። በአካባቢው ላይ የመብራት መቆራረጥ፣ የውሃ እና የኢንተርኔት ችግር አለ፡፡ እኛ የራሳችንን ትልቅ ጀነሬተር በመጠቀም የተሟላ አገልግሎት በመስጠት እንታወቃለን።
ሎጁ ምን ያህል ባር፣ ሬስቶራንትና የመኝታ ክፍሎችን ይዟል?
መኝታዎቹ… በጐጆ ደረጃ 29 ክፍሎች አሉን። ሁለት እና አንድ ሰው የሚያስተናግዱና የተለያየ መጠን ያላቸው ጐጆዎች አሉ፡፡ በጣም ንፁህና ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ ደረጃቸውን እንደጠበቁ በብሎኬት የተሰሩ ፎቅና ምድር ቤት መኝታዎች ናቸው ያሉን፡፡ በአጠቃላይ ግን 56 የመኝታ ክፍሎች አሉን ደረጃውን የጠበቀ አንድ ባርና ሬስቶራንት አለን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በአካባቢው ተመራጭ ነን፡፡
እንደሚታወቀው የሎጁ ባለቤት የውጭ ዜጋ ናቸው። ኮንሶ ድረስ መጥተው እንዴት ኢንቨስት አደረጉ?
የሎጁ ባለቤት አቶ ፍሬዲ ሄስ ሙሉ በሙሉ የውጭ ዜጋ አይደሉም፡፡ በእናታቸው ኢትዮጵያዊ፣ በአባታቸው የአውስትራሊያ ዜጋ ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ነገር ግን ለትምህርት ወደ አባታቸው አገር ሄደው ለተወሰነ ጊዜ ቆይተዋል፡፡ እዚህ ቦታ ኢንቨስት እንዴት ሊያደርጉ ቻሉ ላልሽው፣ ከዚህ በፊት በማስጐብኘት ስራ ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡
አስጐብኚ ድርጅት አላቸው ማለት ነው?
አዎ! “ሔስ ትራቭል” የተሰኘ አስጐብኚ ድርጅት አዲስ አበባ ውስጥ አላቸው፡፡ እናም ቱሪስቶችን ለማስጐብኘት ወደዚህ ስፍራ ይመጡ ስለነበር፣ ለቱሪስቶች ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴልና ሎጅ አለመኖሩን ከተገነዘቡ በኋላ፣ አካባቢውን ስለወደዱትም ጭምር ይህንን ሎጅ ሊሰሩ ችለዋል፡፡
እርስዎ መቼ ነው ሎጁን በስራ አስኪያጅነት መምራት የጀመሩት?
ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት፣ ሎጁ ስራ የጀመረ ሰሞን ማለት ይቻላል፡፡ ከእኔ በፊት ትንሽ የተንጠባጠቡ አሰራሮች ነበሩ፤ ከመጣሁ በኋላ እየተመካከርን ግቢውንም የበለጠ እያሳመርን ለዚህ አብቅተነዋል፡፡ አሁን ያለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ በጣም መልካም ነው፡፡
የእርስዎ የትምህርት ዝግጅት ከሆቴል አስተዳደር ጋር የተገናኘ ነው?
በእርግጥ የእኔ የትምህርት ዝግጅት ጀነራል ማኔጅመንት ነው፡፡ ነገር ግን በአጫጭር ስልጠናዎችና ሴሚናሮች እውቀቴን ከሆቴል ማኔጅመንት ጋር በማቆራኘት ውጤታማ እየሆንኩ ነው፡፡
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የኮንሶ የእርከን ስራ፣ ባህላዊ መንደሮቻቸውና “ኒውዮርክ” የተሰኘው ቦታ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ በኋላ፣ በከተማዋ ያለው የቱሪስት ፍሰት ምን ይመስላል?
እውነቱን ለመናገር ኮንሶ በዩኔስኮ ከተመዘገበችና ዓለም ካወቃት በኋላ፣ የቱሪስቱ ፍሰት በጣም ጨምሯል፡፡ ምናልባት የቱሪስቱ ቁጥር በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ጨምሮ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እኛ ከዚያ በፊት የምናየው እንግዳና በአሁኑ ወቅት የምናየው ይለያያል፡፡ እርግጥ እናንተ የመጣችሁበት ወቅት የግንቦት መጨረሻ “ሎው ሲዝን” የሚባለው ስለሆነ፣ ብዙ ቱሪስት አልተመለከታችሁ ይሆናል። ልክ ከአንድ ወር በኋላ ክረምቱ አካባቢ “ሃይ ሲዝን” ይመጣል፡፡ ያን ጊዜ ለአይን የሚያታክት ቱሪስት ይኖራል፡፡ አጠቃላይ እንቅስቃሴው ይሄን ይመስላል።
ከቱሪስቱ መጨመር ጋር የከተማዋ እድገትና የነዋሪዎቿ ህይወት ላይ የሚታይ ለውጥ አለ?
ወደ እናንተ ሎጅ እየመጡ ለመዝናናት የሚደፍሩስ የከተማዋ ነዋሪዎች አሉ?
ይሄ ጥሩ ጥያቄ ነው! ቀደም ሲል ሎጁ ደረጃውን ጠብቆና አምሮ ስለተሰራ ወደዚህ መጥቶ ለመዝናናት የማይቻል እንደሆነ ነበር ነዋሪዎች የሚገምቱት። በዚህ የተነሳ ሰው ይፈራና ይርቅ ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ባደረግነው አንዳንድ እንቅስቃሴ ማለትም ወደከተማዋ እንግዶች ሲመጡ አብረው የሚመጡ ሰዎችን ስናስተናግድና ስናለማምድ አሁን የሁሉም መዝናኛ ሆኗል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ላይም መጠነኛ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡
ህዝቡ ባለው አገር በቀል እውቀት ነው በዓለም ቅርስነት እርከኖቹንና ባህላዊ መንደሮቹን ያስመዘገበው ስለዚህ አሁን የተለያዩ ለውጦች ይታያሉ፡፡ በእኛ ሎጅ እንኳን ብትመለከቺ፣ በቋሚና በጊዜያዊነት የተቀጠሩ በርካታ ሰራተኞች ህይወታቸውን እያሻሻሉ ነው፡፡
ለምን ያህል ሰራተኞች የሥራ ዕድል ተከፍቷል?
ግንባታው አሁንም እየተካሄደ ነው፤ ግማሹ ግንባታ ማስፋፊያ እየተካሄደበት ሲሆን፤ ግማሹ ደግሞ የቀድሞው ግንባታ ማጠናቀቂያ ላይ ነው። ሎጁ በ34ሺህ 450 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው፡፡ ለ35 ቋሚ ሰራተኞችና ከ50-60 ለሚደርሱ የቀን ሰራተኞች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡ ከሰራተኞቹ 99 በመቶዎቹ የኮንሶ ተወላጆች ናቸው፡፡
አጠቃላይ ግንባታው ምን ያህል ወጪ ፈጀ?
እንዳየሽው ግንባታው ገና አልተጠናቀቀም። ነገር ግን እስካሁን ባለው ሂደት ከ16 እስከ 17 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ ከዚህ በኋላ ለማጠናቀቂያው ምን ያህል ብር ሊፈጅ እንደሚችል መገመት ያዳግታል፡፡
የሎጁን መጠሪያ “ካንታ” ብላችሁታል፡፡ ምን ማለት ነው?
ካንታ ያልነው በአንድ ትልቅ መንደር ውስጥ ያለ ሌላ አነስ ያለ መንደር ለማለት ነው፡፡

           ስፔን የሻምፒዮናነት ክብሯን ማስጠበቅ ሳትችል በምድብ ማጣርያ ከተሰናበተች በኋላ በርከታ የውጤት ትንበያዎች እና ግምቶች ተበላሽተዋል፡፡ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ አዲስ ሻምፒዮን ይጠበቃል፡፡ ከስፔን መሰናበት በኋላ 20ኛው ዓለም ዋንጫ ለብራዚል 6ኛ፤ ለጣሊያን አምስተኛ፤ ለጀርመን አራተኛ፤ ለአርጀንቲና እና ለኡራጋይ ሶስተኛ፤ ለእንግሊዝ እና ለፈረንሳይ ሁለተኛ የሻምፒዮናነት ክብር ትበቃለች ወይንስ በታሪክ 9ኛው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ቡድን ይፈጠራል? የእግር ኳስ ውጤቶች ለግምት እና ለትንበያ አስቸጋሪ ቢሆኑም  ከ20ኛው ዓለም ዋንጫ በተያያዘ ዋንጫውን ማን እንደሚያሸንፍ የተደረጉ ልዩ ጥናቶች፤ የዳታ ስሌቶች እና የንፅፅር ሁኔታዎች ከመቼውም ግዜ በላቀ ሁኔታ ተስተውለዋል፡፡
የምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ዙር 16 ጨዋታዎች ከተደረጉ በኋላ ስፖርት ኢንተለጀንስ የተባለ ድረገፅ በተለያዩ ግምቶች ዓለም ዋንጫን ማን እንደሚያሸንፍ የተሰጡ ትንበያዎችን ትክክለኛነት በመመርመር ልዩ ዘገባ አጠናቅሯል፡፡ የትኛው ግምት ትክክል ለመሆን እንደተቃረበ ግን የጥሎ ማለፍ ምእራፉን መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
የስፖርት ኢንተለንጀንስ ልዩ ሪፖርት ዳሰሳውን በተለያየ መንገድ በተሰሩ 11 ትንበያዎች ላይ አድርጓል፡፡ ከትንበያዎቹ መካከል የተሳታፊ አገራትን የኢኮኖሚ አሃዞች በመተንተን፤በተለያዩ ወቅታዊ የእግር ኳስ ደረጃዎች መነሻነት በተሰሩ ስሌቶች፤ በታሪካዊ ውጤቶች እና በወቅታዊ የቡድኖች ብቃት፤ በየቡድኖቸ ባሉ ተጨዋቾች የዋጋ ግምት እና ጥንካሬ ላይ መሰረት አድርገው የተሰሩ ይገኙበታል፡፡
በስፖርት ውርርድ ተቋማት እና በአቋማሪ ኩባንያዎች የዋንጫው ግምት በአንደኛ ደረጃ ለብራዚል ቢያጋድልም፤ አርጀንቲና፤ ስፔንና ጀርመን በቅደምተከተል ዋንጫውን እንደሚያሸንፉ ግምት ነበራቸው፡፡ በተለያዩ ግምቶች ግማሽ ፍፃሜ እንደምትደርስ በአንዳንዶቹም ዋንጫውን በማሸነፍ የሻምፒዮናነት ክብሯን እንደምታስጠብቅ የተጠበቀችው ስፔን ከምድብ ማጣርያ መሰናበቷ የብዙዎቹን ስሌቶች ትክክለኛነት አጠያያቂ አድርጎታል፡፡ በተለያዩ ሁኔታዎች በተሰሩ 11 ግምቶች እና ትንበያዎች ብራዚል በ9 የዋንጫው አሸናፊ ትሆናለች ተብሏል፡፡ አርጀንቲና ከእነዚህ ግምቶች አንዴ ብቻ የሻምፒዮናነት ግምት ስታገኝ በስምንት ግምቶች ሁለተኛ መሆን እንደምትችል በአንዱ ግምት ደግሞ በ4ኛ ደረጃ ውድድሩን  እንደምትጨርስ ተገልጿል፡፡ ጀርመን በስምንት ግምቶች 3ኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡ በሁለት ግምቶች ዋንጫ እንደምትወስድ የተተነበየላት ስፔን ለግማሽ ፍፃሜ ይደርሳሉ ከተባሉ 4 ቡድኖች ተርታ በተደጋጋሚ መጠቀሳ የብዙዎችን ግምት ፉርሽ አድርጎባቸዋል፡፡
በስፖርት ኢንተለጀንስ ሃተታ መሰረት የዓለም ዋንጫው በሜዳ ላይ ከሚደረገው ፉክክር ውጭ ከሜዳ ውጭ በሚሰራ የተለያየ ስሌት ማን ሊያሸንፍ ይችላል ብሎ በዝርዝር ተንታኔውን አቅርቧል፡፡ በደቡብ አሜሪካ በተዘጋጀ ዓለም ዋንጫ ለግማሽ ፍፃሜ የመድረስ እድል ያላቸው አራት ቡድኖች ብራዚል፤ ጀርመን፤ ኡራጋይ እና አርጀንቲና ሲሆኑ ለዋንጫ ብራዚል እና አርጀንቲነና ተገናኝተው አርጀንቲና ታሸንፋለች፡፡ በፊፋ ደረጃ ዓለም ዋንጫውን ማን ያሸንፍ ከተባለ ደግሞ ለግማሽ ፍፃሜ ብራዚል፤ ጀርመን፤ ስፔንና አርጀንቲና፤ ስፔን ከጀርመን በሚያደርጉት የአውሮፓ ደርቢ ስፔን ታሸንፋለች፡፡ በተጨዋቾች የደሞዝ ክፍያ መጠን ጀርመን በፍፃሜ ጨዋታ ስፔንን ታሸንፋለች፡፡ በአጠቃላይ የቡድን ስብስብ የዋጋ ግምት ብራዚል፤ ፈረንሳይ፤ ስፔንና አርጀንቲና ለግማሽ ፍፃሜ ይደርሳሉ፡፡ ዋንጫውን አሁንም ብራዚል አርጀንቲናን በማሸነፍ ትወስዳለች፡፡

       እያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ ድል  በአጨዋወት ታክቲክ በሚገኝ የበላይነት ይወሰናል፡፡ በየአራት አመቱ የብሄራዊ ቡድኖች የጨዋታ ስትራቴጂ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚታይበት በ20ኛው ዓለም ዋንጫም ተረጋግጧል፡፡ ይሁንና የትኛውም ታክቲክ ከአንድ ዓለም ዋንጫ በላይ በበላይነት መቀጠል አይችልም፡፡ በ1998 እኤአ ላይ በተደረገው 16ኛው ዓለም ዋንጫ አዘጋጇ ፈረንሳይ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው በጠንካራ ፋውሎች በሚታገዝ የመከላከል ጨዋታ  ነበር፡፡
በዚህ አጨዋወት ላይ የዚነዲን ዚዳን ተዓምራዊ አስተዋፅኦ ታክሎበት ዋንጫ የተገኘበት ነበር፡፡ በወቅቱ በዚህ የፈረንሳይ ቡድን ታክቲክ በየጨዋታው በአማካይ 19 ፋውሎችን ይሰራ ነበር፡፡ ከ4 ዓመት በኋላ ግን ፈረንሳይ በሻምፒዮናነት ክብሯን ለማስጠበቅ ገብታ በምድብ ማጣርያ መሰናበት ግድ ሆኖባታል፡፡ በ2002 እኤአ ጃፓንና ደቡብ ኮርያ በጣምራ ባዘጋጁት ዓለም ዋንጫ ላይ የበላይነት ያሳየው ታክቲክ በኳስ ቁጥጥር እና ችሎታ የተመሰረተው የብራዚል የማጥቃት አጨዋወት ነበር፡፡ በዚሁ ዓለም ዋንጫ ብራዚል እስከዋንጫው ባደረገችው ግስጋሴ በየጨዋታው በአማካይ 57 በመቶ የኳስ ቁጥጥር ነበራት፡፡ በ2006 እኤአ  ጀርመን ባዘጋጀችው 18ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ግን የብራዚል ታክቲክ አልሆነለትም፡፡ በምትኩ ጣሊያን በመልሶ ማጥቃት እና በጠንካራ ተከላካይ መስመር የተቀናጀ ቡድን ይዛ በመቅረብ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን በቃች፡፡
ከ4 ዓመት በፊት  ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 19ኛው ዓለም ዋንጫ ደግሞ ኳስን ተቆጣጥሮ በዝግታ በአጫጭር ቅብብሎች የሚተገበረው የስፔን ቲኪ ታካ አጨዋወት የሻምፒዮናነቱን መንበር ተረከበ፡፡  ከዚህ የዓለም ዋንጫ ድል በፊት እና በኋላ የስፔን ቲኪ ታካ ለ6 ዓመታት የዓለምን እግር ኳስ ተቆጣጥሮ ቆይቷል፡፡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫው የሻምፒዮናነት ክብርን በሁለት ተከታታይ የዓለም ዋንጫዎች የማኸነፍ ክብረወሰን ለማስመዝገብ የቀረበችው ስፔን በቲኪ ታካው አጨዋወት አልሆላትም፡፡ በሁለት የምድብ ጨዋታዎች በሆላንድ 5ለ1 እንዲሁም በቺሊ 3ለ0 በመሸነፍ  ከውድድር ውጭ ሆናለች፡፡ ቲኪ ታካ ዘመን ያለፈበትና፤ በብዙ ጎል ልዩነት ለመሸነፍ ምክንያት የሚሆን አጨዋወት ሆነ የስፔን ብሄራዊ ቡድን ላለፉት ስድስት ዓመታት ቲኪታካ በተባለው አጨዋወት የዓለምን እግር ኳስ በአስተማማኝ ውጤት መቆጣጠሩ እርግጥ ነበር፡፡ በ2008 እና በ2012 እኤአ ሁለት የአውሮፓ ዋንጫዎችን እንዲሁም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ማሸነፍ የተቻለው በቲኪ ታካ  አጨዋወት ነበር ፡፡ የስፔን ቲኪ ታካ ፍፁም የበላይነት ባሳየባቸው ጊዜያት በተለይ ከ2006 እስከ በ2009 እኤአ  በ35 ጨዋታዎች በተከታታይ ባለመሸነፍ  ካስመዘገበው ሪከርድ ባሻገር በ15 ጨዋታዎች በማሸነፍ ከብራዚል ቡድን ጋር ዓለም አቀፍ ክብረወሰን ተጋርቷል፡፡ ይሄው የቲኪ ታካ ቡድን ከ2009 እሰከ 2013 እኤአ በ29 ጨዋታ አልተሸነፈም ነበር፡፡ ስፔን ከ4 ዓመት በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት የተካሄደውን 19ኛውን ዓለም ዋንጫ ስታሸንፍ በሽልማት እና በተለያዩ የገቢ ድርሻዎች ያገኘችው 81 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ የዓለም ዋንጫው ድል የስፔን ተጨዋቾችን ተፈላጊነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎ ስብስቡ እስከ 921 ሚሊዮን ዶላር የዋጋ ተመን ነበረው፡፡
የቲኪ ታካ አጨዋወት በዓለም ዋንጫው ከፉክክር ውጭ የሆነው በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችም ነው፡፡ በስፔን ብሄራዊ ቡድን አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች እድሜያቸው ከ30 ዓመት አልፏል፡፡ 8 ተጨዋቾች በብሄራዊ ቡድኑ ማልያ ከ100 ጨዋታዎች በላይ አድርገዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በወጣት ተጨዋቾች በተሞላው እና በፍጥነት ላይ ያተኮረ አጨዋወት በበዛበት ዓለም ዋንጫ የሚያወጣ አልነበረም፡፡
20ኛው ዓለም ዋንጫ  በክለብ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ስማቸው የገነኑትን እነ አርሴን ቬንገር፤ ፔፔ ጋርዲዮላ፤ ጆሴ ሞውሪንሆ፤ ካርሎ አንቸሎቲ፤ ዲዬጎ ሲሞኔ እና ሌሎች ምርጥ አሰልጣኞችን ባያሳትፍም በምርጥ የቡድን አመራር የተካኑና ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎችን እያሳየን ነው፡፡
በ32 ብሄራዊ ቡድኖች ከሚገኙ አሰልጣኞች የብራዚሉ ስኮላሬ፤ የራሽያው ካፔሎ፤ የስፔኑ ዴል ቦስኬ፤ የሆላንዱ ቫንጋል እና የጀርመኑ ጆአኪም ሎው በሰሯቸው ቡድኖች ውጤታማ ለመሆን በከፍተኛ ደረጃ የአጨዋወት ታክቲክ ተከትለው ፉክክር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ በፊት በታክቲክ ደረጃ 4-2-3-1 አሰላለፍን ብዙዎቹ ብሄራዊ ቡድኖች በማሳየት የውድድሩን የፉክክር ደረጃ በመከላከል ላይ በተመሰረተ አጨዋወት ያደበዝዙታል  ተብሎ ከመሰጋቱም በላይ ጎን ለጎን ግን  2 -5- 3 የተባለው አሰላለፍም ተመራጭ እንደሚሆን ይገለፅ ነበር፡፡
የጀርመን ሙሉ እና ውጤታማ የቡድን እንቅስቃሴ፤ የስፔን ቲኪ ታካ፤ በሜሲ የሚመራው የአርጀንቲና የማጥቃት ጨዋታና ፈጣኑ የብራዚል ጎል ወረራ የዓለም ዋንጫው ድባብ ይሆናሉ ተብሎም ተወርቷል፡፡ ተከላካዮች እና አማካዮች ግባቸውን ዘግተው በመከላከል ላይ የተመሰረተ ሂደት የሚከተሉት አጨዋወትና ሁሉም ተጨዋቾች ሙሉ ሜዳ በመሸፈን የሚከተሉት የሆላንድ ቶታል ፉትቦል አጨዋወትም  በአንዳንድ ቡድኖች ይተገብራሉ የሚል አስተያየትም ይሰጥ ነበር፡፡ ከሁሉም ግን በኮንፌደሬሽን ካፕ፤ በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና በሌሎች ትልልቅ ውድድሮች እንደታየው በዓለም ዋንጫውም የመልሶ ማጥቃት ጨዋታ የውድድሩን ሂደት ይቆጣጠረዋል የሚለው ግምት  ያመዘነ ነበረ፡፡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የውጤት የበላይነት ያገኙት ብሄራዊ ቡድኖች ያሳዩት አጨዋወት በክንፍ መስመር ላይ ባመዘነ ፈጣን የማጥቃት ጨዋታ ነው፡፡ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ላይ የተመሰረተው ታክቲክ በግራ እና ቀኝ ተመላላሽ መስመር ላይ የሚጫወቱ ሁለት ተጨዌቾች እና ፈጣን አጥቂዎችን በማሰለፍ ይተገበራል፡፡
አሰልጣኞቹ ስንት ይከፈላቸዋል?
ከዓለም ዋንጫው 32 ተሳታፊ ብሄራዊ ቡድኖች በአገራቸው ዜጋ የሚሰለጥኑት 16 ሲሆኑ ከእነሱ መካከል 9 በአውሮፓ ቡድኖች የሚሰሩ ናቸው፡፡ ሌሎቹ 16 ብሔራዊ ቡድኖች ዋና አሰልጣኞቻቸውን ከአገራቸው ውጭ ቀጥረዋል፡፡ በዓለም ዋንጫው በአገር ደረጃ 5 ጀርመናዊያን አሰልጣኝ መሳተፋቸው ከፍተኛው  ብዛት ሲሆን 3 ጣሊያናዊያን   3 አርጀንቲናውያን 3 ፖርቱጋላውያን አሰልጣኞች እንዲሁም ሶስት ኮሎምቢያዊ አሰልጣኞችም ይገኛሉ፡፡  ከ32ቱ አሰልጣኞች  ሰባቱ የሌላ አገር ዜግነት ይዘው በየብሄራዊ ቡድኑ ተቀጥረው በዓመት ከ3.36 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚከፈላቸው ናቸው፡፡ የራሽያ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ጣሊያናዊው ፋብዮ ካፔሎ በ11.3 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ደሞዛቸው የዓለም ዋንጫው ከፍተኛ  ተከፋይ አሰልጣኝ ናቸው፡፡
በደሞዛቸው ከፍተኛነት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት የእንግሊዝ አሰልጣኝ ሮይ ሆጅሰን ሲሆኑ ከካፔሎ በ2 እጥፍ አንሰው በ5.9 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ደሞዝ ነው፡፡ የጣሊያኑ ሴዛር ፔራንዴሊ በ4.3 ፤ የብራዚሉ ሊውስ ፍሊፕ ስኮላሬ በ4.03፤ የስዊዘርላንድ አሰልጣኝ የሆኑት ጀርመናዊው ኦትማር ሂትዝቫልድ በ3.69፤ የጀርመኑ ጆአኪም ሎው በ3.5፤ የስፔኑ ዴል ቦስኬ በ3.4 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ደሞዝ ተከታታይ ደረጃ ይዘዋል፡፡
በዓለም ዋንጫው ዝቅተኛውን ደሞዝ በመከፈል የመጨረሻ ደረጃ የተሰጣቸው ደግሞ የሜክሲኮው አሰልጣኝ ሲሆኑ ዓመታዊ ደሞዛቸው 206.4 ሺህ ዶላር  ነው፡፡ ከዓለም ዋንጫው አሰልጣኞች ዝቅተኛ ክፍያ የሚያገኙት የየአገሮቻቸውን ቡድን የሚያሰለጥኑት እና በተለይ ደግሞ የአፍሪካን ተወካዮች የሚያሰለጥኑት ሲሆኑ ክፍያቸው ከ252ሺ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር በዓመት ነው፡፡ የጋናው ክዋሲአፒያህ በ252 ሺ ዶላር  እንዲሁም የናይጄርያው ስቴፈን ኬሺ በ391 ሺህ ዶላር  ዓመታዊ ደሞዝ የሚሰሩ ናቸው፡፡

Saturday, 21 June 2014 14:42

ጎል ለምን በዛ?

20ኛው ዓለም ዋንጫ በጎል ብዛት የተንበሻበሸ ሆኗል፡፡ ትናንት ከምድብ 4 የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በፊት በተደረጉት 23 ግጥሚያዎች ላይ 66 ጎሎች ከመረብ አርፈዋል፡፡ በአማካይ በአንድ ጨዋታ 2.87 ጎሎች ማለት ነው፡፡ ዓለም ዋንጫ በ32 ቡድኖች በሚደረጉ 64 ጨዋታዎች መካሄድ ከጀመረ ወዲህ በየውድድሩ አንድ ጨዋታ አማካይ የጎል ብዛት 2.5 ነው፡፡  በ2002 እኤአ ላይ 2.5፤ በ2006 እኤአ 2.3 እንዲሁም በ2010 እኤአ 2.3 ጎሎች በአንድ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ በአማካይ ሲመዘገብ ነበር፡፡  ለጎሎች መብዛት የተለያዩ ምክንያቶችም እየቀረቡ ናቸው፡፡ ብራዙካ የተባለችው ኳስ አመቺነት፤ የቡድኖች አጨዋወት በአመዛኙ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ መሆኑ፤ በርካታ ምርጥ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች በየብሄራዊ ቡድኖቻቸው አስገራሚ ብቃት ማሳየታቸውና የብራዚል ስታድዬሞች ማራኪ ድባብ ይጠቀሳሉ፡፡ ብራዚላዊ ዚኮ  በዓለም ዋንጫው ጎሎች የበዙት የየብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ግብ እንዳይቆጠርባቸው ከመከላከል ይልቅ አስቀድመው በማግባት ለማሸነፍ በተከተሉት ታክቲክ መሆኑን አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ብዙዎቹ አሰልጣኞች የቡድናቸውን አጨዋወት በማጥቃት ላይ እንዲመሰረት ማድረጋቸውን ታዝቢያለሁ ብሏል ዚኮ፡፡ የጎሎች መብዛት የዓለም ዋንጫውን የፉክክር ድባብ አድምቆታል፡፡ በበየጨዋታው አጓጊ ድራማዎችና ልብ ሰቃይ ትእይንቶች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡
በኮከብ ግብ አግቢነቱ ፉክክር ሶስት ተጨዋቾች በሶስት ጎሎች ተያይዘዋል፡፡ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር እና ሆላንዳውያኑ ሮበን ቫን ፕርሲ እና አርያን ሩበን ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ሁለት ጎሎች ያስመዘገቡት 7 ተጨዋቾች ደግሞ   የብራዚሎ ኔይማር፣ የአውስትራሊያው ቲም ካሂል፣ የኮሎምቢያው ጀምስ ሮድሪጌዝ፤ የክሮሽያው ማርዮ ማንዱዚክ፣ የፈረንሳዩ ካሬም ቤንዜማ፤ የአይቬሪኮስቱ ጀርቪንሆ እና የኡራጋዩ ሊውስ ሱዋሬዝ ናቸው፡፡



የፊፋ  ሽልማትና ቦነሶች
ለሽልማትና ለክለቦች ክፍያ በፊፋ የተዘጋጀው 576 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በ19ኛው ዓለም ዋንጫ ከነበረው በ37% ጨምሯል፡፡  ተጨዋቾቻቸውን ለሚያሳትፉ ክለቦች  ፊፋ 70 ሚሊዮን ዶላር እንደየደረጃው የሚከፍል ሲሆን ይኸም ከ4 ዓመት በፊት ከነበረው በ75 % ጭማሪ ታይቶበታል፡፡ ፊፋ በዓለም ዋንጫው ለሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖች ለዝግጅት የሚሆን አስቀድሞ  1.5 ሚሊዮን ዶላር  ከመስጠቱም በላይ በውድድሩ ተሳታፊነት ብቻ ለ32ቱ አገራት ለእያንዳንዳቸው 8 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላቸዋል፡፡ በገንዘብ ሽልማቱ ዝርዝር አከፋፈል መሰረት ዋንጫውን የሚያሸንፍ 35 ሚሊዮን ዶላር ሲከፈለው  ፤ ለሁለተኛ 25ሚ ዶላር፤ ለሦስተኛ ደረጃ 22 ሚሊዮን ዶላር ለ4ኛ ደረጃቨ 20 ሚሊዮን ዶላር  ይበረከታል፡፡ በሩብ ፍፃሜ የሚሰናበቱ 4 ቡድኖች እያንዳንዳቸው 14 ሚ. ዶላር ፤በጥሎ ማለፍ የሚሰናበቱ 8 ቡድኖች ለእያንዳንዳቸው 9 ሚ ዶላር እንዲሁም ከምድብ ለሚሰናበቱ 16 ቡድኖች 8ሚ.ዶላር ይከፋፈላል፡፡
የማበረታቻ ቦነስ እና ሌሎች ክፍያዎችን ለመስጠት ላለፉት 6 ወራት በየአገሩ ቃል ሲገባ ነበር፡፡  የስፔን ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች  የሻምፒዮናነት ክብራቸውን ካስጠበቁ በነፍስ ወከፍ 979ሺ ዶላር እንደሚታሰብላቸው ቃል መገባቱ  ከፍተኛው ቦነስ ነበረ፡፡ በትልልቅ ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ግምት እየተሰጠው ብዙ  ለማይቀናው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንም  ለዋንጫ ድል የቀረበው ቦነስ ለእያንዳንዳቸው 587ሺ ዶላር ነው፡፡
 በአዘጋጇ ብራዚል  448ሺ ዶላር ቦነስ እንደምትሰጥ ሲገለፅ ለፈረንሳይ ቡድንም በተመሳሳይ መጠን  ቀርቧል፡፡ በጀርመን  408ሺ ዶላር ፤  በአሜሪካ 405ሺ ዶላር  እንዲሁም በሆላንድ ደግሞ 371ሺ ዶላር ቦነስ ለእያንዳንዱ ተጨዋች በነፍስ ወከፍ  ለመስጠት ተዘጋጅቷል፡፡
በማበረታቻ የቦነስ ክፍያዎች ዙሪያ በተለይ ብሔራዊ ቡድኖች እና ፌደሬሽኖቻቸው ከፍተኛ ውዝግብ መግባታቸው የተለመደው በአፍሪካ ነው፡፡ የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በፌደሬሽን በኩል ስለሚሰጣቸው ክፍያ ውዝግብ ገብተው የምንፈልገው ካልተሟላ ልምምድ እናቆማለን ብለው መነጋገርያ ሆነዋል፡፡ በመጨረሻም የካሜሮን እግር ኳስ ፌደሬሽን ለእያንዳንዱ ተጨዋች በዓለም ዋንጫው አጠቃላይ ተሳትፎ 91.5ሺ ዶላር በመመደብ ውዝግቡን ሲያበርድ የተጨዋቾቹ ፍላጎት እስከ 160ሺ ዶላር ነበር፡፡  የጋና ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በበኩላቸው በየጨዋታው በሚያስመዘግቡት ድል የሚሰጣቸው የቦነስ ክፍያ 30% አስቀድሞ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡

Page 6 of 18