ዝቅተኛ መሆን አሳሳቢ ሆኗል


የ5ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ኢትዮጵያ በ53 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች ብዛት ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም 10ኛ መሆኗን ተምሬአለሁ፡፡ ዛሬ በሥራ ዓለም ከ20 ዓመት በላይ ቆይቼ ቁጥሩ ያው ከመሆኑም በላይ የወተትና የወተት ተዋጽኦ በጥራትም ሆነ በብዛት ዝቅተኛ መሆኑ ሰሞኑን ተገለፀ፡፡
ኢትዮጵያ ካላት 53 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች 10 ሚሊዮን ያህሉ የወተት ላሞች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ላሞች ውስጥ 98 በመቶ ያህሉ አገር በቀል ዝርያ ያላቸው ናቸው፡፡ አንድ የምትታለብ ላም በቀን በአማካይ የምትሰጠው ወተት ከ 1 ሊትር ተኩል እስከ 1 ሊትር ነው፡፡ የተዳቀሉት ላሞች በቀን በአማካይ 8 ሊትር ወተት ይሰጣሉ፡፡ በአገሪቷ ካሉ የወተት ላሞች በዓመት የሚገኘው ወተት 4 ቢሊዮን ሊትር እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 95 ሚሊዮን ይሆናል ብለን ብንገምት አንድ ኢትዮጵያዊ በዓመት በአማካይ የሚያገኘው የወተት መጠን 19 ሊትር ብቻ ሲሆን፣ የአንድ አፍሪካዊ የወተት ፍጆታ 27 ሊትር ተኩል ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት አንድ ሰው በዓመት መጠጣት አለበት ብሎ የወሰነው 75 ሊትር ወተት እንደሆነ ከትናንት በስቲያ በወተትና ወተት ውጤቶች ጥራትና ደህንነት ላይ ለመምከር በሀርመኒ ሆቴል በተዘጋጀው ወርክ ሾፕ ላይ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ያለባትን የወተት ክፍተት የምትሸፍነው ከውጭ አገር የወተት ውጤቶችን በማስገባት ሲሆን ለዚህም በዓመት 10 ሚሊዮን ዶላር ያህል ውጪ እንደምታደርግ ታውቋል፡፡
በዓመት የሚመረተው የወተት መጠን ማነስ ብቻ አይደለም ችግሩ፤ የጥራቱም ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በመላ አገሪቱ በዘመናዊ ዘዴ የሚመረተው ወተት ከመቶ 10ሩ ብቻ ነው። 90 በመቶው የሚመረተው በኋላቀሩ ባህላዊ የአመራረት ዘዴ በመሆኑ ጥራቱ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ወተት የሚታለብበት ዕቃ፣ ማስቀመጫው፣ ለማቀነባበር ወደ ፋብሪካ ሲወሰድ በየደረጃው ጥራቱ እየተጓደለ ነው፡፡
የወተት ጥራት የሚጓደለው በዚህ ብቻ አይደለም፡፡ ወተት ዱቄት ይጨመርበታል፣ የምትታለበው ላም ጤነኛ መሆኗ በየዓመቱ ምርመራ ስለማይደረግላት ቲቢ ከያዛት ከብት የታለበ ሊሆን ስለሚችል ለጤና ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ወተት 87 በመቶ ውሃ ነው፡፡
አሁን ከእጥረቱ የተነሳ ለገበያ የሚቀርበው ወተት ብዙ ውሃ ተደባልቆበት ስለሆነ የፕሮቲን እጥረት ይከሰታል፡፡ በፕሮቲን እጥረት የተነሳ በአገሪቷ ከሚወለዱ ሕፃናት 64 በመቶ ያህሉ በዕድገታቸው ቀጫጫ እንደሚሆኑ የሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ም/ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ጉታ አመልክተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጥራቱና ደህንነቱ ያልተጠበቀ ወተት ተጠቃሚዎች ለሞት ለሚዳርግ በሽታ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

Saturday, 27 June 2015 09:27

የግጥም ጥግ

ችጋር
አላፊ፣ አግዳሚው - ወጪና ወራጁ
የሰልፍ ተክተልታይ - ወደ ‘ሚሻው ሂያጁ
ነውና ምሳሌው፡-
እሾህ ለአጣሪው -ወንጀል ለፈራጁ፡-
ምስለተሰንካዮች - የሚግበሰበሱ
እንደ ምንጭ ሲፈልቁ - እንደ ‘ኋ ሲፈሱ
ቀለብ ሰፋሪያቸው ከቶ ማነው እሱ?
ሸክሎች ተሰብስበው አፈር እየላሱ፡፡
አንድስ‘ንኳ
በመስቀል ውዥንብር - በቁርባን ቱማታ
በመሃይም ቦታ፡-
የባልቴቶች ጌታ፡-
በግዝት ቅብጥርጥር፡-
በፍታት ድንግርግር፡-
ሚስጥረ ሥላሴ፤
ግዕዝ ወቅዳሴ፡-
በሰንበቴ ጉርሻ፤
በሙት ዓመት ቁርሻ
ባለትልቅ ድርሻ፡-
ከበሮ አስደግፈው አነጣጥረው በልክ፤
ወረብ አስተማሯት ውሽማዬን ብልክ
በመቋሚያ ሽብርክ፤ ቅዳሴ የ’ንብርክ፡፡
በካሣሁን ወ/ዮሐንስ
ከአማርኛ የግጥም መድብል የተወሰደ

Published in የግጥም ጥግ

ፕሮፌሰር መርጋ በቃና፤ አባባሉ ለኢህአዴግ እንደማይሰራ ያውቁታል
ሰማያዊ ፓርቲ በምርጫ ማግስት ሊ/መንበሩንና ምክትሉን አስገመገመ

   ሰማያዊ ፓርቲ በምርጫው ማግስት ባደረገው ግምገማ በእጅጉ ተደምሜአለሁ፡፡ (መደመም እኮ ተወዷል!) ያውም ደግሞ -- በተመሳሳይ ሰዓት “ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ አይደለም” የሚል በቁጣ የታሸ ተቃውሞ ለምርጫ ቦርድ፣ ለኢህአዴግና ለዓለም እያቀረበ፡፡ (ቁጣውን ከግምገማ ማምታታት ግን አላስፈለገውም!) በቅድመ ምርጫ ወቅት በ93 ሚ. ብር የምርጫ በጀት የታማው ሰማያዊ ፓርቲ፤ በምርጫ ማግስት ምክትል ሊቀመንበሩን በ10ሺ ብር ምዝበራ ጠርጥሮ መገምገሙን ሰማን፡፡ (የምዝበራ የፈረንጅ አቻው Embezzlement መሆኑን ልብ በሉ!)  
እኔ የምለው ግን----ኢህአዴግስ የምርጫ ማግስት ግምገማ አድርጓ ይሆን? (በተለይ የፋይናንሷን ነገር!) ለነገሩ ምርጫን በ100 ፐርሰንት አሸንፎ፣ እንደነሰማያዊ በገንዘብ ማጉደል መገምገም ሞራል ይነካል፡፡  (ሙድ ያበላሻል!) እናላችሁ… በአዲስ አበባ በምርጫው 2ኛ የወጣው ሰማያዊ፤ ምንም እንኳን የምርጫውን ውጤት ፈጽሞ እንደማይቀበል ቢገልጽም በዚህ ሰበብ የፓርቲውን መደበኛ ሥራ አላስተጓጎለም፡፡ (በቀጥታ ወደ ግምገማ ነው የገባው!)
በነገራችን ላይ --- ያ ፈጽሞ መስማት የማንሻው ምርጫን ታኮ በዜጎች ላይ የሚደርስ እስርና ወከባ፣ዱላና ስቃይ፣ መፈናቀልና መሰደድ ወዘተ-- በምርጫው ማግስት ሳናስበው ከች ማለቱ አሳዝኖናል፡፡ “በምርጫው አንድም ዜጋ አይሞትም” ያልነው የመፈክር አባዜ ተጠናውቶን አልነበረም። እናላችሁ-- ምርጫ 2007ን ሸወድናት ብለን ስለታችንን ልናገባ ነበር፡፡ ግን አልሆነም። መጀመሪያ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ተገደለ ተባለ፡፡ ትንሽ ቆይቶ መድረክ መግለጫ አወጣ፡፡ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዜና፣ መድረክ በትግራይና በሃድያ ሁለት አባላቱ እንደተገደሉበት ጠቁሞ፣ በምርጫው ማግስት የፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት በኢህአዴግ ካድሬዎች የሚያስመርር ወከባና ስቃይ፣ ድብደባና እስር እንዲሁም ማስፈራሪያና ዛቻ  እየደረሰባቸው እንደሆነ በመረጃ አስደግፎ አስቀምጧል፡፡ (መንግስትና ህግ የት ናቸው?!)
አንዳንድ የመንግስት መ/ቤት ለሁነኛ ጉዳይ ስትሄዱ---ምን ይገጥማችኋል መሰላችሁ? (ምንም!) ከምሬ ነው---ምንም አይገጥማችሁም! ሥራ አስኪያጁን ፈልጌ ነበር? የሉም! ምክትሉስ? እሳቸውም የሉም! ጸሃፊዋስ? አልመጣችም! ህዝብ ግንኙነቱስ? እሱም ወጥቷል! (“ወይ ጭንቂ” አሉ ትግሬው ቢጨንቃቸው!) ግራ ግብት ብሏችሁ---ዘበኛውን ታዲያ ማን ነው ያለው? ስትሉት፣ አንድ የሆነ ሠራተኛ ከውስጥ የተቆለፈ የቢሮ በር ከፍቶ ይወጣና-- ሁሉም ሥልጠና ላይ መሆናቸውን ነግሯችሁ እሱም ቢሮውን ቆልፎ ይከንፋል፡፡ (የሥልጠና ሰዓት ረፍዶበት ሳይሆን አይቀርም!)
እርግጠኛ ነኝ መንግስትና ህግ ግን አገርን ጥለው ሥልጠና አይገቡም፡፡ እኔ እርግጠኛ ብሆንም አንዳንዴ የምንሰማው ግን ጥርጣሬ ውስጥ ይከተናል፡፡ እናላችሁ---መድረክ በምርጫው ማግስት በአባላቶቼ ላይ ደረሰ ብሎ የዘረዘራቸው በደሎች እኮ አምስተኛ ዙር ምርጫ አካሄደች ከምትባል አገር አይጠበቅም፡፡ ሰበቦቹ ደግሞ አስፈሪና አደገኛ ናቸው፡፡ መድረክ እንደሚለው፤ አባላቱ ለዚህ ሁሉ ግፍና በደል የተዳረጉት--- ለምን ለመድረክ ቀሰቀሳችሁ? ለምን ለተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ሆናችሁ? ወዘተ-- በሚል ነው፡፡ (መንግስት ተለወጠ እንዴ?)
እኔ የምለው---ኢህአዴግ ምርጫውን በ100 ፐርሰንት ማሸነፉን ያልሰሙ ካድሬዎች አሉ እንዴ? (ወድጄ እኮ አይደለም!) በምርጫ ሙሉ በሙሉ አሸንፈሃል ከተባሉ ወዲህ---የወከባውና የእስሩ ጋጋታ ምንድነው? (ቁጭት ነው ትቢት?)
በነገራችን ላይ እስካሁን ለሞቱት ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣መንግስት ሃዘኑን አለመግለፁ ያልሆነ ጥርጣሬ ውስጥ ከቶኛል፡፡ (ኢህአዴግ ምርጫውን ማሸነፉን አላመነም እንዴ?) ለምን መሰላችሁ … ምርጫውን ማሸነፉን ካመነ መንግስትነቱን ያምናል። መንግስትነቱን ካመነ ደግሞ የቆመው ለዚህ ወይም ለዚያ ወገን ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን በሙሉ እንደሆነ ባያምን እንኳን ያውቃል (ለደገፈውም ለተቃወመውም!) በዚህ የተነሳ ነው በምርጫው ማግስት ለሞቱት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሃዘኑን መግለጽ ያለበት፡፡ ሃዘኑን መግለጽ ብቻም አይደል። ገዳዮቹን ለፍርድ ለማቅረብ ቁርጠኝነቱን በይፋ መግለጽ አለበት፡፡ ግድያው ፖለቲካዊም ሆነ የግል ጸብ---ለውጥ የለውም (ሁለቱም  ወንጀል ነው!)
በተለይ በአገሪቱ ላይ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እተክላለሁ ለሚል (ቢያንስ በመርህ ደረጃ!) እንደ ኢህአዴግ ያለ ፓርቲ፣ (ከምርጫ ውጤት በኋላ የአቋም ለውጥ ተድርጓል እንዴ!) የተቃዋሚው ጎራ በካድሬ ሲታመስ ሃይ ማለት ይገባው ነበር (የህልውና ጉዳይ ነዋ!)
እናላችሁ … የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በተቃዋሚነታቸው ባይወዳቸው እንኳ ሊጠላቸው አይገባም (መንግስት ነዋ!) ግፍና በደል ያውም እስከ ግድያ ሲደርስባቸውም፣ “መንግስት ስሆን የሁሉም ነኝ” ብሎ አጋርነቱን ማሳየት ነበረበት፡፡ “ግድያው ከፖለቲካ ጋ አይገናኝም” ምናምን ዓይነት መልስ ውሃ አያነሳም፡፡ (መንግስትና ህግ ያለበት አገር መስሎኝ?)
እኔ የምለው … ምርጫ ቦርድ “Mission accomplished!” ብሎ ቢሮውን ከረቸመ እንዴ? ተቃዋሚዎች በምርጫ ማግስት አባላቶቻችን ተገደሉብን ሲሉ (ባያመለክቱ እንኳን) ለመመርመር፣ ጉዳዩን ለማውገዝ---ጣልቃ ለመግባት --- ምነው ድምጽና አቅም አጣ? ምርጫ ቦርድም እንደ መንግስት ሁሉ፣ የሁላችንም እንጂ የዚህ ወይም የዚያ ወገን አይደለም ብዬ እኮ ነው፡፡ (ከሆነ ንገሩኝ!)
በመጨረሻ ህይወታቸውን ላጡት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ (ኢትዮጵያውያን ማለት ይቀላል!) ነፍስ ይማርልን ብዬ በመነሻዬ ወደጀመርኩት ገራገር ወግ እመለሳለሁ (የጨዋታዬን መስመር ስለሳትኩ ግለ ሂሴን ውጫለሁ!)
እናላችሁ…ሰማያዊ በምርጫው ማግስት በራሱ ላይ ባካሄደው “ምህረት የለሽ” ግምገማ የፓርቲውን ሊ/መንበር ኢንጂነር ይልቃልን በዳተኝነት፣ (በምርጫ ቅስቀሳ ሽርሽር ሄደዋል …በሚል!) ም/ሊቀመንበሩን ደግሞ በገንዘብ ማጉደል ወንጅሏል (ኧረ ዲሞክራሲያዊነት!) በእስከዛሬው የጦቢያ ተቃዋሚዎች እውቀቴ፤  የፓርቲ ፕሬዚዳንቶች ወይም ሊ/መንበሮች በስልጣን ላይ እያሉ ሲገመገሙ ሰምቼም አይቼም አላውቅም (በህልሜም እንኳን!) ድንገት ከተገማገሙም (ከተቧቀሱ ማለት ይሻላል!) የማታ ማታ (ቦርዱ ቢኖርም  ባይኖርም!) ፓርቲው መፍረሱ አይቀርም፡፡ እስካሁን በግምገማ ንክችት ያላለው (ከ92 ወዲህ ማለቴ ነው !) ኢህአዴግ ብቻ ነው! (ያደገበት ነዋ!)
 እናላችሁ --- የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበሩ፤ “የምርጫ ግብረሃይል ሆነው ሲሰሩ ከፓርቲው 10ሺ ብር ያህል ገንዘብ መዝብረዋል?”፣ “በእጩ ተወዳዳሪዎች አመላመል ላይ አሻጥር ሰርተዋል” በሚል  ሲገመገሙ በብስጭት ስብሰባውን ረግጠው ወጥተው ነበር። (“የማይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል አሉ!”) ወጥተው ግን አልቀሩም፡፡ ምስጋና ለም/ቤቱ አባላት ሸምጋዮች ይሁንና---ተገምጋሚው ወደ ስብሰባው ተመልሰው ገቡ (በግምገማ ኩርፊያ የለም!) ከዚያም 10ሺ ብር መዝብረዋል የተባለውን በተመለከተ ም/ሊቀመንበሩ ከማስተባበል ይልቅ አስተዛዘኑ፡፡ “10ሺ ብር መዝብረሃል ከተባልኩ ከየትም ተበድሬ ለፓርቲው ተመላሽ አደርጋለሁ” አሉ፡፡ (ይሁና!) ለነገሩ የፓርቲው አባላትም ቦንብ ቦንብ የሆኑ የግምገማ ቃላትን ነው የተጠቀሙት፡፡ (ከጥፋቱ ጋር የማይመጣጠን !)
እናላችሁ … ሌሎችም ፓርቲዎች የምርጫ ማግስት ግምገማቸውን አድርገው ውጤቱን ቢነግሩን ምን ይለናል፡፡ አያችሁ----ተቃዋሚዎች ፓርላማ ባይገቡም፣ የመንግስት ሥልጣን ባይጨብጡም ግልጽነታቸውን፣ ዲሞክራሲያዊ አሰራራቸውን ወዘተ--ለራሳቸው እየተለማመዱ ለህዝብም ቢያሳውቁ እምነትና ልብን በጊዜ ለማሸነፍና ለመግዛት ያግዛል፡፡  
በነገራችን ላይ ዘንድሮ ኢህአዴግ፣ ምርጫውን በ“ዝረራ” ያሸነፈውን ያህል፣ ተቃዋሚዎችም (አንጋፋዎቹን ማለቴ ነው!) ውጤቱን በ“ዝረራ” አልተቀበሉትም፡፡ ምነው ሲሏቸው---- ፍትሃዊነት፣ነጻነት፣ተዓማኒነት-- ይጎድለዋል ሲሉ ጣታቸውን ወደ ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ ይሰነዝራሉ፡፡ 50 ገደማ አባላትን ይዞ ከተፍ ያለው የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን በበኩሉ፤ “ምርጫውን ሰላማዊ፣ የተረጋጋና ተዓማኒነት ያለው ነው” ቢልም “free and fair የሚል ነገር ትንፍሽ አላለም” እያሉ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ (ንፉግ በሉት!) እኛ ግን እድሜ ለአገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ጥምረቶቻችን፡፡ 40 ሺ ታዛቢዎችን በትኖ ምርጫውን እንዲታዘቡ አድርጓል። (40 ሺ ውጤት እንዳትጠብቁ!) በአጭሩ፤ “ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ነበር”ብሎ ተገላግሏል፡፡ (ጣጣ ፈንጣጣ የለም!)
አንድ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ ወዳጄ፣ የኢህአዴግን ፓርላማውን ለብቻው መቆጣጠር ሲሰማ ምን አለ መሰላችሁ? “እንኳንም የዩኒቨርሲቲው የታሪክ ዲፓርትመንት ተዘጋ” “ለምን እንደዚያ አልክ?” ብዬ ጠየቅሁት ግራ በመጋባት፡፡ ወዳጄም፤ “አንዳንድ ታሪካችን የነጮች መሳለቂያ ስለሚያደርገን በታሪክ ዶሴ ባይካተት ይሻለናል” አይለኝ መሰላችሁ፡፡ (ይሁንለታ!)
አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ ደግሞ “የዩኒቨርሲቲው ሂስትሪ ዲፓርትመንት የተዘጋው የኢትዮጵያ ታሪክ የተጻፈው በአሸናፊዎች ስለሆነ እሱን ለማረም ነው” የሚል ማብራሪያ ከኢህአዴግ ሹማምንት መስማቱን ነግሮኝ ስገረም ሰነበትኩላችሁ፡፡ (ማን ይሆን የታሪካችን ኤዲተር?)
እኔ የምለው ግን ---- የዓለም ታሪክ ራሱ የአሸናፊዎች አይደለም እንዴ? ኢህአዴግ ደርግን አሸነፈ። “ተራራ የሚያንቀጠቅጥ ትውልድ” በማነው የተጻፈው? በኢህአዴግ እኮ ነው- በአሸናፊው ወገን፡፡ ይኼውላችሁ ታሪክ መጻፍ አይደለም---- ኑሮውን የሚኖሩትም እኮ አሸናፊዎቹ ናቸው! (ምርጫን በ100 ፐርሰንት ላሸነፈ ፓርቲ ይሄ ግልጽ ነው!)
 እስኪ አንድ ጥያቄ ልወርውር፡ (ሎሚ አይደለም፤ ጥያቄ ነው!)
የዘንድሮን ምርጫ ታሪክ ማን ቢጽፈው ጥሩ ነው? (ሂስትሪ ዲፓርትመንት የለማ!)
ሀ-አሸናፊው
ለ- ተሸናፊው
ሐ- ምርጫ ቦርድ
መ- ወጣት ሊግ
ሠ- ፓርላማው   
ለማንኛውም ግን አንዳንድ ተቃዋሚዎች የዘንድሮን ምርጫ እያሰላሰሉ -- ምንአልባት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ከበረታባቸው ፈጽሞ እጅ እንዳይሰጡ! ባይሆን-- የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢው ፕ/ር መርጋ በቃና የተናገሩትን እያስታወሱ ለመፅናናት ይሞክሩ፡፡ (ምን ነበር ያሉት?) “የምርጫው ውጤት የዓለም መጨረሻ አይደለም … የዛሬ 5 ዓመት  ምርጫ ይኖራል”  (ያፅናናል ያልኩት ሆድ የሚያስብስ ነው ለካ!)
 በነገራችን ላይ ፕሮፌሰሩ ይሄን ያሉት---ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ አይደለም ብለው ለተነጫነጩባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነበር፡፡ ግን ይሄንኑ አባባል ለኢህአዴግ (ለአውራው ፓርቲ ማለቴ ነው!) ሊደግሙት የሚችሉ ይመስላችኋል? እንበል-- ተቃዋሚዎች በአብላጫ ድምጽ ቢያሸንፉና ቅሬታ አቅራቢ ኢህአዴግ ቢሆን፣ ፕ/ሩ ብድግ ብለው፤ “ኢህአዴግዬ ---- የአለም መጨረሻ እኮ አይደለም---” ምናምን ሲሉ አልታያችሁም? (ቦርዱ ቀውጢ ይሆን ነበር!)
*አቧራውን ለማጥራት (ምርጫ ቦርድን በስሱ ጎሸም ያደረግሁት፣ ለተንኮል ሳይሆን ለራሱ ለቦርዱ ስል ነው፡፡
አያችሁ---አንዳንድ ተቃዋሚዎች “ቦርዱ የማይነቀፍ፣ የማይተች፣ የማይከሰስ፣ አትኩንኝ ባይ ተቋም ሆኗል--”በማለት ሲከሱት ስለሰማሁ፣ ውሸታቸውን ለማጋለጥ ብዬ ነው፡፡ ወደፊትም እቀጥልበታለሁ!)

       በፈርኦን ዘመን የነበሩ ህዝቦች ለአስማት ጥበብ (Magic) ያላቸው አወንታዊ አመለካከት በጣም ከፍተኛ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ለአስማተኞች የሚሰጡት አድናቆትና ከበሬታ ሲበዛ ልዩ ነው፡፡ ከዚያም ነበር አምላክ ሙሴን ወደ ህዝቡ ሲልከው፣ ቅድሚያ የአስማት ጥበብን የሰጠው፡፡ አምላክ ይህን ጥበብ ለሙሴ መስጠቱ የወቅቱን ህዝብ ቀልብ ለመግዛት የሚያስችል መሳሪያ መሆኑን በማወቁ ነው፡፡
ሙሴ የተሰጠውን የአስማት ጥበብ ተላብሶ ወደ ፈርኦን ህዝብ ሄደ፡፡ ፈርኦን ግን ማንንም በአስማት ጥበባቸው ማዋረድ የሚችሉ፣ እሳት - የላሱ አስማተኞችን ሰብስቦ ከሙሴ ጋር አጋፈጣቸው። የሙሴ ሀቀኝነት የሚረጋገጠው (አምላክን ተገዙ የሚለው) አስማተኞቹን መርታት ከቻለ ብቻ እንደሆነ ፈርኦን በአደባባይ አወጀ፡፡ በመሆኑን በሙሴና በአስማተኞቹ መካከል ውድድር ለማድረግ ቀጠሮ ተያዘ፡፡ ህዝቡ በዚህ ልዩ ውድድር ላይ እንዲገኝ ግብዣ ተደረገለት፡፡ የቀጠሮው ቀን እንደደረሰ የግብፅ ህዝብ ንቅል ብሎ በመውጣት  ክቡን የውድድር ሜዳ አጨናነቀው፡፡ ፈርኦንና የርሱ የቅርብ ባለስልጣናት የክብር ቦታቸውን ያዙ፡፡ ሙሴና አስማተኞቹ ብትራቸውን እንደያዙ እንደቆሎ በፈሰሰው ህዝብ መሐል ፊት ለፊት ተፋጠጡ፡፡
ሙሴ ጥበባቸውን እንዲያሳዩ ቅድሚያ ለአስማተኞቹ እድሉን ሰጠ፡፡ የፈርኦን አስማተኞች ህዝቡን በኩራት እየተንጎራደዱ ካዩ በኋላ የያዙትን በትር መሬት ላይ ሲጥሉት ከበትርነት              ተለውጠው የሚፍለከለኩ እባቦች ሆነው ታዩ። ይህን ትእይንት አሰፍስፎና አንገቱን አስግጎ ሲመለከት የነበረው ህዝብ በጣም ተደንቆ ጩኸቱን አቀለጠው።
ተራው የሙሴ  ነበርና እሱም የያዘውን በትር ወደ መሬት ጣለ፡፡ ትልቁ ጥበብ የታየው እዚህ ላይ ነበር፡፡ ሙሴ የጣለው በትር ወደ ትልቅ እባብ ተለውጦ የአስማተኞቹን ትንንሽ እባቦች እየለቃቀመ ዋጣቸው፡፡ በአስማተኞቹ ጥበብ ገና ተደንቆ ያልጨረሰው ህዝብ፤ ሙሴ ባሳየው ተአምር አፉን ከፍቶ ቀረ፡፡ ቀጥሎ የፈርኦንን ቆሽት እርር - ድብን ያደረገ ጭብጨባና ፉጨት ህዝቡ አሰማ፡፡ ሙሴ የህዝዱን ቀልብ መግዛት ብቻ ሳይሆን፣ አስማተኞቹ ራሳቸው ለአምላክ ለመገዛት እንዲንበረከኩ አደረገ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ የህዝቡን ቀልብ ለመግዛት የተጠቀመው ልክ እንደሙሴ የአስማት ጥበብን አልነበረም፡፡ በሙሴ ዘመን የነበረው ጥበብ ለኢየሱስ ዘመን ህዝቦች እንደማይሰራ አምላክ ያውቃል፡፡ በኢየሱስ ዘመን የእስራኤል ህዝቦችን ይዞ ሲፈታተን የነበረው ትልቁ ነገር በሽታ ነበር፡፡ በመሆኑም ኢየሱስ የህክምና ጥበብን ይዞ መጣ፡፡ ለምጣሙን፣ ሽባውን፣ አይነ - ስውራኑን እና በሌሎች ደዌ የሚሰቃዩ በሽተኞችን በመፈወስ ህዝቡን መሳብና ማስደነቅ ቻለ፡፡ ከዚህም በላይ የሞቱ ሰዎችን በማስነሳት ትልቁን የህክምና ፈውስ አሳየ፡፡  ኢየሱስ በዚህ የህክምና ጥበቡ በርካታ ሰዎችን ተከታይ ማድረግ ቻለ፡፡
ነብዩ መሐመድ አረቦች እንዲከተሏቸው ለማድረግ ልክ እንደ ሙሴ አስማትን፣ እንደ ኢየሱስ የህክምና ጥበብን አልተጠቀሙም፡፡ በነብይ ዘመን የነበሩ አረቦች ለቋንቋና ስነ-ፅሁፍ ያላቸው ፍቅር በጣም የበዛ ነው፡፡ በዚህ ወቅት አረቦች በአደባባይ ላይ እየተሰባሰቡ የውዳሴ ግጥሞችን ያቀርቡ ነበር፡፡ እንዲሁም የንግግር ክህሎት ያላቸው አረቦች በሰዎች ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ነበራቸው፡፡ ነብዩ መሐመድ እነዚህን ሰዎች ለመዋጋትና ወደ አምላክ ለማቅረብ የተጠቀሙት በቋንቋና ስነ- ፅሑፍ የበለፀገውን ቁርአን ነበር፡፡ በርካታ አረቦች በቁርአን ተደመው ነብዩ ይዘውት በመጡት እስልምና ውስጥ ገቡ፡፡ በቁርአን ቋንቋ፣ ስነ-ፅሁፍ እና መልእክት የተሸነፉት አረቦች፤ ቁርአን የአምላክ ስራ እንጂ በሰው ልጅ አቅም እንደማይሞከር በማረጋገጣቸው ለነብዩ አገዛዝ እጅ ሰጡ፡፡
ቅዱስ ቁርአን የወረደው አሁን በያዝነው በተከበረው የረመዳን ወር ላይ ነበር፡፡ ሙሴ ከፈርኦን ህዝቦች ጋር በአስማት ጥበብ እንደተዋጋው፣ ኢየሱስ ከበሽታና ከሞት በፈወሰው የህክምና ጥበቡ የህዝቦችን ቀልብ እንደሳበው ሁሉ፣ ነብዩ ሙሐመድም በቁርአን ቋንቋና ስነ - ፅሁፋዊ ጥበብ ከአረቦች ጋር ግብግብ ገጥመዋል፡፡ አምላክ እንደየዘመኑና እንደ ህዝቦች ፍላጎት ለሶስቱም፣ ሶስት የተለያዩ ጥበቦችን ሰጥቷል፡፡
ነብዩ ሙሐመድ በሒራ ዋሻ ውስጥ ለብቻቸው ተገልለው ለብዙ ጊዜ ስለአምላክና ስለሰው ልጆች ያስላስሉ (Meditation) ነበር፡፡ አንድ ቀን በዚህ ዋሻ ውስጥ ሳሉ፣ መላኢኩ ጂብሪል  (ገብርኤል) በሰው አምሳል ተከስቶ ወደ ዋሻው በመግባት፣ አላህ ለነብይነት እንደመረጣቸው አበሰራቸው፡፡ ከዚያም “አንብብ!” አለ ጂብሪል ለነብዩ፡፡ “እኔ ማንበብ አልችልም” ሲሉ ነብዩ በፍርሐት እየተርበተበቱ መለሱ፡፡ ጂብሪል ነብዩን ጭምቅ አድርጎ ከለቀቃቸው በኋላ በድጋሚ “አንብብ!” አላቸው፡፡ በፍርሐት የራዱት ነብዩ፤ “ማንበብ አልችልም” ሲሉ በድጋሚ መለሱ፡፡ ጂብሪል አሁንም ጨምቆና አስጨንቆ ከለቀቃቸው በኋላ ለመጀመሪ ጊዜ የወረዱን አምስት የቁርአን አንቀፆች አንብቦላቸው ተሰወረ፡፡
“አንብብ፤ በዛ ሁሉን በፈጠረው ጌታህ ስም
ሰው ከረጋ ደም በፈጠረው፤
አንብብ፤ ጌታህ በጣም ቸር ሲሆን፤
ያ በብዕር ያስተማረ
ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ፡፡”
(አል - ዐለቅ፣ 1-5)
ቁርአንን ልዩ የሚያደርገው የቋንቋ አጠቃቀሙ፣ መልእክቱና ስነ - ፅሁፋዊ ውበቱ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ አቅም እሱን የመሰለ መጽሐፍ ማቅረብና የማይቻልና የማይታሰብ መሆኑ ጭምር ነው። ነብዩን ሲያወግዙና ሲያስተባብሉ የነበሩት ቁረይሾች፣ ቁርአንን የመሰለ አንቀፅ አቅርበው ከነብዩ ጋር መወዳደር እንደሚችሉ አላህ መድረኩን ክፍት አደረገላቸው፤ እንዲህ በማለት፡-
“ሰዎችም፣ ጋኔኖችም የዚህን ቁርአን ብጤ ለማምጣት
ቢሰበሰቡ፤ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳት ቢሆኑም እንኳ፤
ብጤውን የመሰለ አያመጡም በላቸው፡፡”
(አል - ኢስራእ፣ 88)
ቁርአንን የመሰለ መጽሐፍ ማቅረብ ለአረቦች ከባድ መሆኑን ያወቀው አላህ፤ ውድድሩን ወደ አስር ምዕራፍ በማውረድ ያቀለዋል፡፡
“ይልቁንም ቁርአንን ቀጣጠፈው ይላሉን?፡- እውነተኞች እንደሆናችሁ ብጤውን የሆነ አስር የተቀጣጠፉ ምዕራፎች አምጡ፤ ከአላህ ሌላ የቻላችሁትን ረዳት ጥሩ በላቸው፡፡”
(ሁድ፣ 13)
አስር ምዕራፎችን ማቅረብ ለአረቦች ከባድ በመሆኑ አላህ አሁንም ውድድሩን የበለጠ አቅልሎ፣ አንድ ምዕራፍ አምጥታችሁ ነብዩን ተወዳደሩ ይላቸዋል፡፡
“በባሪያችን ላይ ካወረድነው (አንቀፆች) በመጠራጠር ውስጥ ከሆናችሁ ከብጤው አንዲት ምዕራፍ አምጡ፤ እውነተኞች ከሆናችሁ ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ።”
(አል-በቀራህ፣23)
ጥንታዊ አረቦች በቋንቋና ስነ - ፅሑፍ የተካኑ በመሆናቸው ነብዩ ካመጡት ቁርአን ጋር ለመወዳደር ሲሉ በርካታ ስነ - ፅሑፎችን ፈብርከዋል፡፡ አልተሳካላቸውም እንጂ፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ ራሱን እንደ ነብይ አድርጎ በርካታ አረቦችን ያጭበረበረው ሙሳይሊማህ ይገኝበታል። ሙሳይሊማህ ልክ እንደ ሙሐመድ ለኔም ራዕይ ወርዶልኛል በማለት ስንኞችን ይቋጥር ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ የቁርአን አንቀፆችን ወስዶ በራሱ ቃላት እየተካ ያቀርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የአል-ከውስር ምዕራፍን ተጠቅሞ የራሱን “ራዕይ” ፈብርኮ ነበር፡-
“እኛ በጣም ብዙ፣ በጎ ነገሮችን ሰጠንህ (የጀነት ወንዝ - አል - ከውስር) ስለዚህ ለጌታህ ስገድ፤ (በስሙ) መስእዋትም አቅርብ”
(አል - ከውስር፣ 1-3)
ሙሳይሊማህ ከላይ የቀረበችውን የቁርአን አንቀፅ እንዲህ አድርጎ ቀየራት፡-
“በእርግጥ እኛ የጀነት ቁልፎችን ሰጠንህ
ስለዚህ ለጌታህ ስገድ፣ እረፍትም አድርግ”
አንድ ቀን ጨመር ኢብን አል - አስ የተባለ የአረብ ቁረይሽ ወደ ሙሳይሊማህ ዘንድ በመሄድ “እኔ ትክክለኛው ነብይ ማወቅ ስለምፈልግ ላንተ የወረደ ራዕይ ካለ ንገረኝ?” ይለዋል፡፡ ሙሳይሊማህ፤ “በአሁን ሰዓት ለሙሐመድ የወረደ አንቀፅ ይኖር ይሆን?” ሲል ዐመርን ጠየቀው፡፡ ዐመር፤ “በጣም አጭር እና እጥር - ምጥን ያለች ምዕራፍ ወርዳለታለች” በማለት ሱራ አል-ዐስርን ያነብለታል፡-
በጊዜያት እምላለሁ
ሰው ሁሉ በእርግጥ በኪሳራ ውስጥ ነው፡፡
ከነዚያ ያመኑትና መልካም ከሰሩት፤ በእውነትም
አደራ የተባባሉት፤ በመታገስም አደራ የተባባሉት ብቻ ሲቀሩ፡፡”
     (አል - ዐስር)
ብልጣ - ብልጡ ሙሳይሊማህ ለቅፅበት አእምሮውን ካሰራ በኋላ “ለኔም እኮ ራዕይ ወርዶልኛል” አለው፡፡ የሙሳይሊማህ “ራዕይ” በግርድፍ ትርጉም ይህን ይመስላል፡-
አንቺ ዋበር ሆይ!
አንቺ ዋበተር ሆ!
ሁለቱ ጆሮ ‘ቺሺ
እንዲሁም ደረትሺ
መኖሪያ መመኪያዎችሺ
በተቀረው ኋላሺ
ከመቆፈር በቀር ምንም መላ የለሺ  
የመሳይሊማህ አጭበርባሪነት ግልፅ የሆነለት ዐመር ደንግጦ ዝም አለ፡፡ ሙሳይሊማህ ግን “ስለወረደልኝ ራዕይ ምን ታስባለህ?” ሲል የደነገጠውን ዐመር ጠየቀው። ዐመር እንዲህ አለ፡- “በጌታ ይሁንብኝ ውሸትህን ማወቄን፣ አንተ ራስህ ታውቃለህ፡፡ ወንድሜን ትቼ ወዳንተ መምጣቴ ጥፋቱ የኔ ነው፡፡” በማለት ወደ ነብዩ ሄዶ እስልምናን ተቀበለ፡፡
በእርግጥ ዐመር ቢደነግጥ ያንሰዋል፡፡ ሙሳይሊማህ በግጥሙ ውስጥ ያነሳው፣ ዋበር ስለምትባል ድመት መሳይ እንስሳ ነበር፡፡ ዋበር ትላልቅ ጆሮዎች ያሏት፣ ከኋላዋ ግን አስቀያሚ የሆነች የዱር እንስሳ ነች፡፡ ለነብዩ የወረደችው ሱራ አል - አስር ግን ስለሰው ልጆች እጣ - ፈንታ የምትናገር ነበረች። አላህ ብዙ ጊዜ ራሱ በፈጠራቸው ነገሮች ሲምል በቁርአን ውስጥ እናነባለን፡፡ ለምሳሌ፡- “በተራራዎች እምላለሁ … በፀሐይ እምላለሁ … በንፋስ እምላለሁ …” የሚሉ ገለፃዎች በሌሎች ምዕራፎች ውስጥ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ በአል - አስር ምዕራፍ ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ “በጊዜያት እምላለሁ” ሲል ይጀምራል፡፡ የተቀሩት አንቀፆች ደግሞ የሰው ዘር መዳኛ መንገዶችን ይጠቁማሉ፡፡ በተዘዋዋሪ የጀነት መግቢያ ቁልፎች አራት መሆናቸውን አል - አስር ትናገራለች፡፡
ማመን  
ማመን ብቻ ሳይሆን በተጨማሪም መልካም ስራ መስራት
እውነታን አጥብቆ መያዝ (ለሐቅ ሟች መሆን)
ትዕግስት (ፅናት) ማሳየት (በመከራና ስቃይ ወቅት አምላክን ሳንክድ በትዕግስት መፅናት)
የተጠቀሱትን ያላሟላ ማንኛውም ሰው በኪሳራ ውስጥ መሆኑን አላህ የተናገረበት ምዕራፍ ነች - ሱራ - አል ዐስር፤
“በጊዜያት እምላለሁ
ሰው ሁሉ በእርግጥ በኪሳራ ውስጥ ነው፡፡
ከነዚያ ያመኑትና መልካምን ከሰሩት፤ በእውነትም አደራ የተባባሉት፤ በመታገስም አደራ የተባባሉት ብቻ ሲቀሩ፡፡”
ታዋቂው የእስልምና ህግ ተንታኝ ኢማም ሻፊ‘ኢ ስለዚህች ምዕራፍ እምቅነት ሲገልፁ፤ “አላህ ሌሎቹን የቁርአን ምዕራፎች ባያወርድ እንኳን ሱራ አል - ዐስር ብቻ ለሰው ልጆች መመሪያነት በቂ ነበረች፡፡” በማለት ነው፡፡
ሙሳይሊማህ አንቀፆችን መፈብረክ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ነገሮችም እስልምናን ተፈታትኗል። ነብዩ የመጨረሻ ህመማቸው በጠናባቸው ወቅት ሙሳይሊማህ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ላከላቸው፡-
ከሙሳይሊማህ - የአላህ መልዕክተኛ
ለሙሐመድ - የአላህ መልዕክተኛ
“መልካም ዜና ልንገርህ፡፡ እኔም እንዳንተ ነብይ በመሆኔ ግማሹን የአረቢያ ምድር ለኔ፣ ግማሹን ደግሞ ላንተ ይሁንና እንከፋፈል፡፡ …”
ነብዩ ሙሐመድ የሚከተለውን መልስ ላኩለት፡-
ከአላህ መልዕክተኛ - ሙሐመድ
ለውሸታሙ - ሙሳይሊማህ
“ምድር የአምላክ ነች፡፡ እርሱ ለሚፈልገው ይሰጣል፤ ሁልጊዜም አሸናፊ የሚሆኑት ደግሞ እርሱን የሚገዙ እማኞች ብቻ ናቸው፡፡ …”
ሁሉንም የነብዩ ደብዳቤ ሳናነብ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ቃላት ብቻ መሳይሊማህን የሚያንኮታኩቱ ነበሩ። “ምድር - የአምላክ - ነች፡፡”
“ምድርን እንከፋፈል” እና “ምድር የአምላክ ነች” በሚሉት ቃላቶች መካከል ሁለት ተቃራኒ አለሞችን እናያለን፡፡ ይኸውም የሙሳይሊማህ ቁሳዊነትንና የነብዩ መንፈሳዊነትን ናቸው፡፡
ነብዩ ሙሐመድ ከሞቱ በኋላ ቢሆን የሙሳይሊማህ አደገኛነት ጨምሮ ለእስልምና አገዛዝ ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ ነበር፡፡ አል - ያማማህ በተባለ ታሪካዊ ጦርነት ላይ የቁርአን ሀፊዞችን እየመረጠ በመግደል፤ ቁርአን ለቀጣይ ትውልዶች እንዳይተላለፍ ለማድረግ ሞክሮ ነበር፡፡ ይህ የሙሳይሊማህ ክፉ ተግባር ቁርአን በጥራዝ መልክ መቀመጥ እንዳለበት የመጀመሪያውን የሙስሊሞች ከሊፋ ጠቁሞታል፡፡ ከሊፋ አቡበከር በሙሐመድ 23 የነብይነት ዓመታት ውስጥ ቁርአንን በአእምሯቸው የሸመደዱ (ሐፊዞች) ሱሐባዎች፤ በጦርነት ከማለቃቸው በፊት ቁርአንን በመጽሐፍ መልክ እንዲያዘጋጁ ትእዛዝ ሰጠ። 114ቱንም ምዕራፎች የሸመደዱት እነኝህ ሱሐባዎች ነብዩ በህይወት ሳሉ በድንጋይ፣ በቆዳ፣ በቅጠሎች ላይ የፃፏቸውን አንቀፆች አሰባስበው አሁን የምናየውን ቅዱስ ቁርአን ማዘጋጀት ቻሉ፡፡
ሙሳይሊማህ፣ ከሊፋ አቡበከር ከላከበት የሙስሊሞች ጦር ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ ካደረገ በኋላ በመጨረሻ በካሊድ ጦር ተደመሰሰ፡፡ እሱም ተገደለ። ነገር ግን ሙሳይሊማህ፣ በአል - ያማማህ ጦርነት ላይ 450 ሐፊዞችን፣ 300 የነብዩ የልብ ጓደኞችን ገድሎ ነበር፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 27 June 2015 09:24

የፀሐፍት ጥግ

ረመዳን ወደ ገፅ 19 ዞሯል
• የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ድረገጽን ባለፈው ዓመት በአጠቃላይ ከ80
ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ጎብኝተውታል፡፡
• ዘንድሮ ከጥር ወር እስከ መጋቢት አጋማሽ ባሉት ጊዜያት ብቻ ከ20
ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች የተመለከቱት ሲሆን በየወሩ በአማካይ
ከ6 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች አሉት፡፡
• እስካሁን የተጠቀሱት መረጃዎች የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ብቻ
የሚመለከቱ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣
በአረብ አገራትና በሌሎች ዓለማትም በርካታ ሚሊዮን
ኢትዮጵያውያን የሚጎበኙት ተወዳጅ ድረ-ገጽ ነው!
• ሦስት ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ የሚገኙ የዜና ድረ-ገጾችን
በተለያዩ መስፈርቶች አወዳድረው፣ የአዲስ አድማስ ድረ-ገጽን
ከቀዳሚዎቹ ሦስት ድረገጾች አንዱ መሆኑን መስክረውለታል፡፡
• በአሁኑ ሰዓት ትላልቅ የሪል እስቴት ኩባንያዎች፣ዓለም አቀፍ
የሞባይል ስልክ አምራቾች፣ታዋቂ የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካዎችና
ሌሎችም---- በድረ ገጻችን ላይ እያስተዋወቁ ይገኛሉ፡፡
እርስዎስ? ለእርስዎም ቦታ አለን!!
ድረ ገጻችንን ይጎብኙት፡ www.addisadmass.news.com
ለተጨማሪ መረጃ፡- 0911-936787
ድርጅትዎን፣ ምርትዎንና አገልግሎትዎን
በርካታ ሚሊዮኖች በሚጎበኙት
ድረ-ገጻችን ያስተዋውቁ!
• አርታኢ እና አሳታሚ በሚሉት መጠሪያዎች
መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ከፈለግህ:-
አርታኢ ረቂቅ ጽሑፎችን የሚመርጥ ሲሆን
አሳታሚ አርታኢዎችን የሚመርጥ ነው፡፡
ማክስ ሹስተር
• መጽሐፍ በኪስ ውስጥ እንደሚይዙት
የአትክልት ሥፍራ ነው፡፡
የአረቦች አባባል
• ሥነፅሁፍን በራሱ እንደ ግብ አልቆጥረውም።
አንድ ነገር የማስተላለፊያ መንገድ ነው፡፡
ኢሳቤል አሌንዴ
• ፍፅምናን ብጠብቅ ኖሮ አንዲትም ቃል
ባልፃፍኩ ነበር፡፡
ማርጋሬት አትውድ
• ረቂቅ ሃሳብ ማስፈር፣ ጥናት ማድረግ፣
ስለምትሰራው ነገር ከሰዎች ጋር ማውራት
- ከእነዚህ ውስጥ አንዳቸውም ከመፃፍ
አይመደቡም፡፡ መፃፍ መፃፍ ነው፡፡
ኢ. ኤል ዶክቶሮው
• ለመኖር ታሪኮችን መተረክ አለብህ፡፡
ዩምቤርቶ ኢኮ
• ስድስቱ የመፃፍ ወርቃማ ህጐች፡- ማንበብ፣
ማንበብ፣ ማንበብ እና መፃፍ፣ መፃፍ፣ …
መፃፍ ናቸው፡፡
ኧርነስት ጌይንስ
• ፀሐፊነት በቋንቋ መስከርን ይጠይቃል፡፡
ጂም ሃሪሰን
• ለወጣት ፀሐፍት ምክር መለገስ ቢኖርብኝ፣
ስለ ጽሑፍ ወይም ስለራሳቸው የሚያወሩ
ፀሐፊዎችን አትስሟቸው እላቸዋለሁ፡፡
ሊሊያን ሄልማን
• በኪነጥበብ ቁጥብነት ሁልጊዜ ውበት ነው፡፡
ሔነሪ ጄምስ
• ማንነትህን እስክታውቅ ድረስ መፃፍ
አትችልም፡፡
ሳልማን ሩሽዲ
• በጥያቄ እጀምራለሁ፡፡ ከዚያም መልስ
ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡
ሜሪ ሊ ሴትል
• ባልሆነ ቦታ ኮማ መደንቀር ያስጠላኛል፡፡
ዋልት ዊትማን
• ስለራስህ እውነቱን ካልተናገርክ ስለሌሎች
ሰዎች እውነቱን ልትናገር አትችልም፡፡
ቨርጂኒያ ውልፍ
• በውስጥህ ያለ ያልተነገረ ታሪክን ከመሸከም
የበለጠ ትልቅ ስቃይ የለም፡፡
ማያ አንጄሎ

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 27 June 2015 09:22

የባህል ጉራማይሌ!

ከውጭ ወዳጆቻችሁ ጋር ላለመቆራረጥ መውሰድ ያለባችሁ ጥንቃቄዎች

    ሁሉም አገሮች የተለያየ ባህልና ልማድ ስላላቸው ሁሉም ዜጋ በአገሩ ባህልና ልማድ ሲስተናገድ ደስ እንደሚለው አያጠራጥርም፡፡ በአገራችንስ የአገሩን በሬ በአገሩ ሰርዶ፣ ወፍ እንዳገሯ ትጮሃለች፣ …. ይባል የለ! ስለዚህ የየአገራቱን ባህልና ልምድ ማወቅ ግንኙነታችሁን የሰመረ ያደርገዋል፡፡ እስቲ የጥቂት አገሮችን ለየት ያሉ የባህል ገጽታዎች እንመልከት፡፡
በሩሲያ፡- ሩሲያዊ ወዳጃችሁን ከአውሮፕላን ጣቢያ ስትቀበሉ፣ ወይም ላደረገላችሁ ውለታ ምስጋና ስታቀርቡ የአበባ ስጦታ ለማበርከት ካሰባችሁ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባችኋል፡፡ ለወዳጆቻችሁ፣ ለጓደኞቻችሁና ለቢዝነስ ሸሪካችሁ፣ … ቢጫና ቀላ ያለ የገረጣ አበባ ፈፅሞ እንዳትሰጡ፡፡
በሩሲያ ባህል ቢጫ አበባ እንደ መጥፎ ገድ ስለሚቆጠር ያንን ዓይነት አበባ በስጦታ ማበርከት ለማጥበቅ ያሰባችሁትን ወዳጅነት ሊያበላሽና ከእነ አካቴውም ሊያቆራርጣችሁ ይችላል፡፡ ቢጫ አበባ በባህላቸው እንደማታለያ ስለሚቆጠር ለስጦታ እንደማይሆን ማወቅ ይገባል፡፡ የገረጣ ቀይ አበባ በሩስያውያን ዘንድ ለስጦታ የማይሆንበት ምክንያት ደግሞ ሰው ሲሞት መቃብር ላይ የሚቀመጥ ወይም ከጦር ሜዳ ለተመለሰ አባት አርበኛ የሚበረከት በመሆኑና የመጥፎ ገድ ምልክት ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡  
በግብፅ፡- በአፍሪካዊቷ ግብፅ፣ ጓደኛችሁ ወይም ወዳጃችሁ እቤቱ ምሳ ወይም እራት ጋብዟችሁ ስትሄዱ የቀረበላችሁ ምግብ ጨው ያነሰው ከሆነ፣ ያላችሁ ብቸኛ አማራጭ አንድም ችሎ መብላት አሊያም ምግቡን ነካ ነካ አድርጎ መተው ብቻ ነው። ምናልባት በአካባቢያችሁ የጨው ዕቃ አግኝታችሁ ምግቡ ላይ ጨው ለመነስነስ ከሞከራችሁ፣ ያን ጊዜ ከወዳጃችሁ ጋር መቆራረጣችሁ ነው፡፡ ምግብ ላይ ጨው መነስነስ ጋባዣችሁን እንደ መስደብና መናቅ ይቆጠራል፡፡
ሌላም ትርጉም አለው፡፡ ምግቡ በመስኖ ሳይሆን የዓመት ዝናብ ጠብቆ ከሚደርስ እህል የተዘጋጀ ከሆነ፣ የምግቡን ጣዕም እንዳልወደዳችሁት ይቆጠራል፡፡ በዚህም የተነሳ ከመልካም ወዳጃችሁ ጋር ልትቀያየሙ ትችላላችሁ፡፡    
በቬኒዙዌላ፡- ኢትዮጵያውያን ቀጠሮ ባለማክበርና በግብዣም ሆነ በስብሰባ ሰዓት አክብረን ባለመገኘት እንታወቃለን፡፡ በዚህም የተነሳ በውጭዎቹ ዘንድ ሳይቀር “የአበሻ ቀጠሮ” በሚለው አባባል ዝነኛ ሆኗል።  ታዋቂው የአገራችን የሙዚቃ ንጉሥ ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ፤
“አርቆ ማሰቢያ እያለን አዕምሮ
እንደምን ተሳነን ለማክበር ቀጠሮ
ቸልተኞች ሆነን ወደኋላ እንዳንቀር
በሁላችንም ዘንድ ቀጠሮ ይከበር”
በማለት ያቀነቀነውም ያለምክንያት አልነበረም። በጥበብ ሊያስተምረን፣ ሊያርቀን ፈልጎ እንጂ፡፡ ግን ምን ያደርጋል? የሚሰማው አላገኘም፡፡  
በእኛ አገር ቢያንስ ቀጠሮ አለማክበር ወይም በተባለው ሰዓት አለመገኘት ስህተት መሆኑ ይታመንበታል፡፡ በቬኒዙዌላ ግን ነገርዬው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ በላቲን አሜሪካዋ ቬኒዙዌላ ለግብዣ የተጠራ እንግዳ በሰዓቱ ከች ካለ ወይም ሌላ ቀጠሮ ኖሮት ሰዓቱን ለማብቃቃት ቀደም ብሎ ከደረሰ በበጎ ዓይን አይታይም፡፡ የምግብ ችግር ያለበት ረሃብተኛ፣ ስግብግብና ሆዳም … ተብሎ ይወገዛል፡፡ እናም በቬኒዙዌላ ግብዣ የተጠራ ሰው፣ ከቀጠሮው ሰዓት 10 ወይም 15 ደቂቃ አርፍዶ ነው የሚደርሰው፡፡ በዚህም የተነሳ ሰዓት አላከበረም ብሎ የሚወቅሰው ማንም የለም፡፡ በባህሉ የሚያስወቅሰውና የሚያስገምተው በተጠሩበት ሰዓት አናቱ ላይ (እቅጩን) መድረስ ነው፡፡ እንዲህም ያለ ጎታች ባህል አለ፡፡  
በቻይና፡- በኢትዮጵያ በተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚሰሩ ቻይናውያን ቁጥር በርካታ ነው፡፡ ከቻይናዊ አባት የተወለዱ ሕፃናት 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ከገቡ ቆዩ‘ኮ፡፡ ስለዚህ ቻይናዊ ጓደኛ ወይም ወዳጅ ያላችሁ ሰዎች ባለማወቅ ስጦታ ስታበረክቱ ግንኙነታችሁ እንዳይሻክርና እንዳይበጠስ የቻይናውያኑን አንዳንድ ልማድና ወግ ማወቅ መልካም ነው፡፡
አንድ ቻይናዊን ለማመስገን ብላችሁ መሀረብ፣ ከእህል ገለባ የተሰራ ሰንደል (ነጠላ) ጫማና አበባ በስጦታ ለማበርከት እንዳትሞክሩ፡፡ ለምን መሰላችሁ? ቻይናውያን እነዚህን ስጦታዎች ከሞትና ከመቃብር ጋር ስለሚያዛምዷቸው እንደ ክፉ ምልኪ ይቆጥሩዋቸዋል። በዚህም የተነሳ ሊጠሏችሁና ሊርቋችሁ ይችላሉ። ስለዚህ ግንኙነታችሁን አጠብቅ ብላችሁ ጭራሽ እንዳታበላሹት መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡
በኖርዌይ፡- እኛ ኢትዮጵያውያን ለፓስታ ካልሆነ በቀር ሹካ አንፈልግም፡፡ ፓስታንም ቢሆን ከእንጀራ ጋር መብላት ለምደናል፡፡ የፓስታን ጣልያኒያዊ ዜግነት የቀየርነው ይመስላል፡፡ ለእኛ በእጃችን መብላት ባህላችን ነው፡፡
አንድ ጊዜ ከአንድ ፈረንጅ ጋር ለስራ መስክ ወጥተን እንደለመድነው ምሳ በጋራ አዘን እንበላለን፡፡ ምሳው እንጀራ ስለነበር ፈረንጁም ሳይወድ በግዱ እንደ እኛው በእጁ ገባበት፡፡ በልተን ስንጨርስ እጃችንን እየታጠብን ሳለ ታዲያ ፈረንጁ፤ “ለመጀመሪያ ጊዜ በጣቶቼ በላሁ” ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡
የኖርዌይ ዜግነት ያለው ወዳጃችሁ ቤት ምሳ ወይም እራት ከተጋበዛችሁ ፈፅሞ በእጃችሁ እንዳትበሉ። በኖርዌይ ባህል መሠረት፤ ሁልጊዜ ቢላዋና ሹካ ከምግብ ጠረጴዛ ላይ አይጠፉም፡፡ የገበታ ሥነ-ሥርዓት ነው ማለት ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ ምግቦች ሳንዲዊች ሳይቀር የሚበሉት በሹካና ቢላዋ ነው፡፡ ባህላቸው በእጅ መመገብን አይፈቅድም፡፡ ባይሆን የቢላና ሹካ አያያዙን ቀደም ብሎ መማር ወይም መለማመድ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡  
በኔዘርላንድ (ሆላንድ)፡- ለኔዘርላንድ ወዳጃችሁ ስጦታ ማበርከት ስትፈልጉ ፈጽሞ የወጥቤት ቢላዋ ወይም እንደመቀስ ሁለት ስለት ያለው መሳሪያ አለመሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባችኋል፡፡  ምክንያቱም በባህላቸው ስለታምና ሹል ነገር በስጦታ ማበርከት እንደመጥፎ ገድ ስለሚቆጠር ነው፡፡
በጃፓን፡- በኢትዮጵያ፣ እንደቻይናውያን ባይሆኑም በተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚሰሩ ጃፓናውያን ብዙ ናቸው፡፡ ታዲያ በሥራም ሆነ በሌላ ከጃፓናውያን ጋር ጓደኝነትና ወዳጅነታችሁ እንዲጠነክር ባህላቸውን አበክሮ ማወቅ ይመከራል።
ጃፓናውያንና የሩቅ ምስራቅ አገሮች ሲመገቡ እንደሹካ የሚጠቀሙበትን ከእንጨት በሚሰራ መቆንጠጫ (ቶፕስቲክ) መጠቆም ወይም ማመልከት፣ መጫወት ወይም ምግብ በጋራ ስትመገቡ፣ የምግቡን ደኅንነት ለመጠበቅ (በንኪኪ ከሚተላለፍ በሽታ ለመከላከል) ቶፕስቲኩን ስትጠቀሙበት በነበረው ጫፍ ሳይሆን አፍ ባልነካው ሌላኛው (ተቃራኒ) ጫፍ መሆን አለበት፡፡ አፍዎ በነካው ጫፍ መጠቀም እጅግ በጣም አስነዋሪ ከመሆኑም በላይ ስለሃይጂን ምንም ግንዛቤ እንደሌለዎት ያስገነዝባል፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ስህተቶች ላለመፈፀም መጠንቀቅ ወዳጅነትንና ግንኙነትን ለማጠንከር ይበጃል፡፡
የውጭ አገራት ባህልን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለማወቅ ጥረት ማድረግ በዕውቀት ማነስ የውጭ ዜጎችን ከማስቀየም ይታደጋል፡፡ ማንም ሰው ወግና ባህሉን ሲያውቁለት ደስ ይለዋልና መልካም ስሜትንም ይፈጥራል፡፡
ምንጭ፡- (Reader’s Digest – June 2015)

Published in ህብረተሰብ

መንግስት ሁሉም ላይ ገናና ሆነ”፤ “ኢንቨስትመንትና የገበያ ኢኮኖሚ አልተስፋፋም

    የኢትዮጵያና የቻይና መንግስታት፣ “በመሃላችን ነፋስ እንዳይገባ” የሚሉ የቅርብ ወዳጆች ይመስላሉ። አንዱ የሌላኛውን ስም በክፉ አያነሳም። አንዱ ሌላውን የሚያስከፋ ቃል አይወጣውም (ኢህአዴግ በአፍላ የስልጣን ዘመኑ፣ የያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ከተናገሯት አንዲት ዓረፍተነገር በስተቀር)።
“የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ እንደግፋለን” ነበር ያሉ አቶ ታምራት። ያኔ፣ ከኢህአዴግ መሪዎች አፍ የማይጠፋ የዘወትር አባባል ነው። ችግሩ ምንድነው? አቶ ታምራት ስለ ታይዋን ነው የተናገሩት።
የቻይና መንግስት ደግሞ፣ በታይዋን ጉዳይ እንዲህ አይነት ነገር መስማት ያሳብደዋል። በታይዋን ጉዳይ ላይ ድርድር አያውቅም። ከቻይና ጋር ለመቆራረጥ ካልፈለገ በቀር፣ የትኛውም መንግስት ለታይዋን የእውቅና ድጋፍ አይሰጥም። ኢህአዴግም ብዙ ሳይቆይ፣ “የራስን እድል... እስከመገንጠል” የሚባለው ነገር ለቻይና አይሰራም በማለት አስተባብሏል። ለቻይና የማይበጅ ከሆነ ለኢትዮጵያስ ታዲያ ለምን?  መጨረሻ ላይ፣ “ስለ ቻይና እኛ ምን አገባን?” በሚል ነው ኢህአዴግ ጉዳዩን በአጭሩ ዘግቶ የተገላገለው። ከአቶ ታምራት ያመለጠው ዓረፍተነገር አልተደገመም።
ከዚያ ወዲህ፣ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲና ኢህአዴግ እርስበርስ ሲደናነቁ ነው የምንሰማቸው፡፡ እንደ ታላቅና ታናሽ ወንድም ናቸው ብንልም ማጋነን አይሆንም። በሁለት በሦስት ዓመት በሚካሄደው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፣ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ሃላፊዎች በተጋባዥነት እየመጡ፡፡ “ጓድ” “ጓድ” ሲባባሉ አይተናል።
ምን ይሄ ብቻ? የኢህአዴግ ካድሬዎች በየጊዜው ቻይና እየሄዱ የፖለቲካና የፓርቲ አደረጃጀት ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ (አስገራሚው ነገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የቻይና መንግስት ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ አይደመጥም። እንደሚመስለኝ የኢህአዴግና የቻይና አይነት ግንኙነት ይመቻቸዋል፡፡ ቅሬታቸው በኢህአዴግ ቦታ እኔ መቀመጥ ነበረብኝ የሚል ነው፡፡)
በአጭሩ የቻይና ወዳጅነት፣ ኢህአዴግ የሚኮራበትና ተቃዋሚዎች የሚመኙት ነገር ነው ልንል እንችላለን፡፡
በዚህ መሃል፣ የቻይና መንግስት ኢህአዴግን በመተቸት ቅሬታ ሲያቀርብ አስቡት፡፡ ትልቅ ዜና አይደለም?
ግን እንደ ትልቅ ዜና ሲወራ አልሰማንም፡፡ ለምን? እሺ… ኢህአዴግ፣ “ከወንድም የቻይና መንግስት” እና “ከቻይና ኮሙኒስት ጓዶች” የተሰነዘረበትን ትችት ለመደበቅ እንደሚፈልግ አያጠራጥርም፡፡ “ገመናዬን አላሳይም” ቢል አይገርምም፡፡ ነገር ግን፣ ኢህአዴግን የሚቃወሙ ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞችና ምሁራንስ ለምን ዜናውን አይተው እንዳላዩ አለፉት? በድንጋጤ ክው ብለው፣ አንደበታቸው ተለጉሞ ይሆን?
እስቲ ይታያችሁ፡፡ “የፌደራል መንግስት በሁሉም ነገር ላይ ገናና ሆኗል” የሚል ትችት ከቻይና በኩል ሲመጣ በዝምታ ይታለፋል? “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእድገት ጐዳና እንዲቀጥል፤ ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚመጣ የግል ኢንቨስትመንትን በአወንታ የሚያስተናግድ አመቺ ስርዓት አልተፈጠረም፡፡ የገበያ ኢኮኖሚ አልተስፋፋም” የሚል ወቀሳ ከቻይና መንግስት ሲሰነዘር ዝም ይባላል?
በቅርቡ የመጡት የቻይና አምባሳደር ይህንን ቅሬታና ትችት ለኢህአዴግ ባለስልጣናት እንዳቀረቡ ዘኢኮኖሚስት መጽሔት ገልጿል - ከምርጫው ማግስት ባወጣው ዘገባው፡፡
ቻይናን እንደ አርአያና እንደ መሪ ኮከብ የሚያዩ በርካታ መንግስታት ቢኖሩም፤ በአፍሪካ ምድር ኢህአዴግን የሚስተካከል እንደሌለ በመግለጽ ነው ዘኢኮኖሚስት ዘገባውን የሚጀምረው፡፡ በዚያው ልክ የቻይና መንግስት በካድሬ ስልጠና፣ በብድር እና በንግድ ዋና የኢህአዴግ አለኝታ ሆኗል፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ የታሰበው ያህል ለውጥ አልመጣም። ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ ባለፉት አምስት አመታት ንቅንቅ አላለም፡፡ ዘንድሮ ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንዲደርስ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ እዚያው 3 ቢሊዮን ደላር ገደማ ላይ ተኝቷል፡፡
ኤክስፖርትን የሚያሳድግ፣ በተለይም ደግሞ በየአመቱ ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ በመቶ ሺ ለሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ከመንፏቀቅ አልፎ ያን ያህልም መራመድ አልቻለም፡፡ ለምን? መንግስት ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የፕሮጀክት እቅዶችን ስላላወጣ አይደለም፡፡
እንዲያውም፣ የመንግስት ፕሮጀክቶች ናቸው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የገነኑት፡፡ ግን እንደተለመደው የመንግስት ፕሮጀክቶችን በመፈልፈል፣ በዚያው መጠን የሃብት ብክነትና ሙስና እንዲስፋፋ ከማመቻቸት ያለፈ ደህና ውጤት እንደማይገኝ ለአስር አመታት ያለ ውጤት የተጓተቱት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
እናም፣ “ፌደራል መንግስት በሁሉም ነገር ላይ ገናና ሆኗል፣ የገበያ ኢኮኖሚ አልተስፋፋም” የሚል ቅሬታና ትችት ቢሰነዘር ተገቢ ነው፡፡ ምናልባት… ትችቱ ከቻይና መምጣቱ አስገራሚ ሊመስል ይችላል፡፡
ነገር ግን አስገራሚ አይደለም፡፡ የቻይና ባለስልጣናት የአገራቸውን ታሪክ ካልዘነጉ በቀር፣ ሁለት ዋና ቁም ነገሮችን ሊስቱ አይችሉም፡፡ ከ40 ዓመታት በፊት፣ ከአፍሪካም የከፋ ድህነት ተዘፍቃ በነበረችው የያኔዋ ቻይና ውስጥ፣ እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በረሃብ ማለቃቸውን ያስታውሳሉ፡፡ እና የቻይና የረሃብ ታሪክ እንዴት ተቀየረ? ይሄ አንደኛው ቁም ነገር ነው። የቻይና መንግስት ዛሬም ድረስ በአገሪቱ ኢኮኖሚ እና በዜጐች ኑሮ ላይ እጅጉን በአገሬም ገናና ቢሆንም፤ ከ40 አመት በፊት ግን በብዙ እጥፍ በሁሉም ነገር ላይ የገነነ እንደነበር አይረሱትም፡፡ ይሄ ሁለተኛው ቁም ነገር ነው። የግል ሃሳብ፣ የግል ንብረት፣ የግል ህይወት የሚባሉ ነገሮችን ጨርሶ ወደማጥፋት ደርሶ ነበር፡፡
“የህብረት ስራ ማህበር”፣ “የልማት ሰራዊት”፣ “የ1ለ5 አደረጃጀት”…በሚባለው አቅጣጫ እስከ መጨረሻው እስከ ጥግ ድረስ እንደመሄድ ማለት ነው፡፡
በያኔዋ ቻይና፣ በቃ…እያንዳንዱ ገበሬ በማህበር ተደራጅቷል፡፡ በግል ማሳ ማረስ፣ ሰራተኛ መቅጠር፣ አምርቶ መሸጥ ቀርቷል፡፡ የእርሻ ማሳ፣ የእርሻ ስራ፣ የእንስሳት እርባታም ጭምር፣ የእርሻ ምርት… ሁሉም የጋራ ሆኗል - የማህበር፡፡ አስተዋይ እና ፈዛዛ፣ ታታሪና ሰነፍ…እንደ እኩል ነው የሚታዩት፡፡ ሁሉም ነገር በማህበር ሆኖ የለ? አስተዋዩና ፈዛዛው በእኩል ድምጽ ውሳኔ ያስተላልፋሉ - ሃሳባቸው እኩል ባይሆንም፡፡ ታታሪውና ሰነፉ እኩል የስራ ሰዓት ያስመዘግባሉ - እኩል ሙያና ታታሪነት ባይኖራቸውም፡፡ እኩል ተሸምተው ምርት ይካፈላሉ - የማምረት ብቃታቸው እኩል ባይሆንም። ከጋራ ምርት ብዙ ድርሻ ለመውሰድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሽሚያ አይገርምም - ይህንን የሚዳኙ ራሽን አከፋፋይ ቢሮክራቶች ይፈጠራሉ፡፡ የጋራ ስራ ላይ ግን የመሻማት ልምድ ሳይሆን የመለገም ልምድ ነው የሚስፋፋው - ይህንን የሚቆጣጠሩ  ካድሬዎች ይፈጠራሉ፡፡
ታታሪና ሰነፍ እኩል ምርት የሚሻሙበትና በስራ መለገምን የሚያስፋፋ ስርዓት በሰፈነባት በያኔዋ ቻይና፣ ድህነት ተባብሶ ሚሊዮኖች በረሃብ አልቀዋል፡፡
ብዙዎቹ ኮሙኒስት ካድሬዎች ለዚህ ደንታ አልነበራቸውም፡፡ እነሱን የሚያስጨንቃቸው ሌላ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ከአንዲት የገጠር መንደር የተላከ መረጃ ምንኛ እንዳስቆጣቸው ተመልከቱ፡፡ የትንሿ መንደር ነዋሪዎች ምን አጠፉ? ገናናው መንግስት ባዘዛቸው መሰረት በማህበር ተደራጅተዋል - ሁሉም ነገር የጋራ ነው ተብሏል፡፡ ነገር ግን፣ በጋራ እየሰሩ በጋራ ምርት የሚከፋፈሉ ይመስላሉ እንጂ፣ በሚስጥር የእርሻ ማሳ ለየብቻ ተከፋፍለው በግል ማረስና ማምረት ጀምረዋል። ለይምሰል ተሰብስበው የስራ እቅድና የምርት ክፍፍል ላይ ውሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡ ነገር ግን የየግላቸውን አቅምና አላማ ይዘው፣ የግል እቅድ እያወጡ ነው የሚሰሩት፡፡ የስራ ተቆጣጣሪ የለም፡፡ ሁሉም ለራሱ ሲል ነው ተግቶ መስራት ያለበት፡፡
የስራ ውጤታቸውንና ምርታቸውንም ይወስዳሉ - ሽሚያ የለም፡፡ ራሽን የሚያከፋፍል ካድሬም አያስፈልጋቸውም፡፡
እንግዲህ ብዙ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ባላት አገር ውስጥ፣ ይሄው የትንሿ መንደር ነዋሪዎች ድርጊት እንደ ትልቅ ወንጀል ተቆጥሮ፣ እንደ ትልቅ የአገር ክህደት ታይቶ ነው ጉዳዩ ለፕሬዚዳንቱ እስከመቅረብ የደረሰው። “አብዮታዊ እርምጃ” እንዲወስድባቸም ሃሳብ ቀርቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ዴንግ ዚያዎፒንግ ውሳኔ ግን፣ “እስቲ፣ ምንም እንዳላወቅን ዝም እንበላቸውና የት እንደሚደርሱ እንያቸው” የሚል ነበር፡፡ እውነትም፣ እየቆየ ሲታይ የመንደሪቷ ነዋሪዎች በክህደት ወንጀል የአገሪቱን መንግስት አላስወገዱም፡፡ ረሃብን ነው ያስወገዱት፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ የአብዛኛው ነዋሪ ምርትና ኑሮ ተሻሻለ፡፡ ፈዛዛው ነዋሪ የአስተዋይ ጐረቤቱን ሃሳብ ስብሰባ ላይ በክፋት በማፍረስ ለመርካት አይጣጣርም። ይልቅስ፣ ከአስተዋይ ጐረቤቱ የመማር እድል ያገኛል፡፡
ሰነፉ ሰውዬ አዳዲስ የዳተኛና የልግመኛ ዘዴዎችን እየፈለፈለ፣ በታታሪ ጐረቤቱ ልፋት ከተገኘው የጋራ ምርት የበለጠ ድርሻ ለመውሰድ የሽሚያ ተንኮል ሲሸርብ አያድርም፡፡ ይልቅስ፣ የታታሪ ጐረቤቱን ምርታማነት እያየ አርአያነቱን ተከትሎ ለስራ የመነሳሳት እድል ያገኛል፡፡
የዚያች መንደር ነዋሪዎች፣ ከጋራ ድህነት ተገላገሉ። ሁሉም እንደየአቅሙና እንደየጥረቱ በግል እያመረተ ህይወቱን የማሻሻል እድል አገኘ፡፡ ዚያዎፒንግ የዛሬ 40 ዓመት የዚህችን መንደር ታሪክ ነው በመላ አገሪቱ እንዲደገምና የገበያ ኢኮኖሚ እንዲስፋፋ መንገድ የጠረጉት፡፡ እስከዛሬም አልተቋረጠም፡፡ እናም የመንግስት ገናናነት ሙሉ ለሙሉ ባይወገድም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ፣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ ባይሰፍንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከግል ኢንቨስትመንት ጋር እየተስፋፋ፤ ቻይና ባለፉት 30 ዓመታት በብልጽግና ጐዳና ትልቅ ለውጥ አስመዘገበች፡፡ ይህንን በቅጡ የሚገነዘብ ሰው፤ የቻይና መንግስት ኢህአዴግን መተቸቱ፣ “የፌደራል መንግስት ገናናነት በዛ”፣ “የገበያ ኢኮኖሚና የግል ኡንቨስትመንት አልተስፋፋም” የሚል ወቀሳ ማቅረቡ አስገራሚ አይሆንበትም፡፡
ደግሞም ካሁን በፊት ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ትችት አይደለም፡፡
ከ25 ዓመት በፊት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ተመሳሳይ ትችት አጋጥሟቸዋል፡፡ ለጉብኝት ወደ ቻይና ያቀኑት ኮ/ል መንግስቱ፣ “ጓድ…ጓዶች…” እየተባባሉ ነው ከቻይና ባለስልጣናት ጋር የተወያዩት፡፡
የጦር መሳሪያ እንደሚፈልጉ የተናገሩት ኮ/ል መንግስቱ፣ የብስክሌት ፋብሪካ ለመክፈትም እርዳታ ስጡኝ የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከቻይና ጓዶች ያገኙት ምላሽ ግን ትችት ነው፡፡  የፕሬዚዳንቱ ተግሳፅም ተጨምሮበታል፡፡ መንግስት የገነነበት የኮሙኒዝም ኢኮኖሚ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች አገራት እንዳልበጀ የገለፁት የቻይና ፕሬዚዳንት፣ ኮሙኒዝምን ከመዘመርና የመንግስት ፋብሪካ ለመክፈት ከመሯሯጥ ይልቅ ለአገርህ የሚበጃት የግል ኢንቨስትመንትና የገበያ ኢኮኖሚ ላይ ብታተኩር ነው የሚል ምክር ለግሰዋል - ለኮ/ል መንግስቱ፡፡ ደግሞስ፣ ተራራ በበዛበት አገር የብስክሌት ፋብሪካ ለመክፈት መሯሯጥ ምን ትርጉም አለው?
ኮ/ል መንግስቱ፣ ከወንድም የቻይና መንግስት በተሰረዘባቸው ትችትና በጓዶች ተግሳፅ አልተደሰቱም፡፡
ግን ጥሩ ምክር ነበር ያገኙት፡፡ አመት ሳይቆይ ነው፤ ዋና የኮሙኒዝም አቀንቃኟ ሶቭዬት ህብረትና አጃቢዎቿ የምስራቅ አውሮፓ መንግስታት በኢኮኖሚ ቀውስ ሲዳከሙ ቆይተው የተንኮታኮቱት፡፡
ቻይና አልተንኮታኮተችም፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው? መንግስት ያልገነነበት የገበያ ኢኮኖሚ፣ ብቸኛው የብልጽግና መንገድ እንደሆነ ያሳየች ቀዳሚዋ አገር አሜሪካ እያለች ቻይናን እንደ ዋና አርአያ ማየት ስህተት ቢሆንም፤ ከቻይና ታሪክ ጠቃሚ ቁምነገር መማር እንችላለን፡፡
“የመንግስት ገናናነነትን መቀነስ፣ የግል ኢንቨስትመንትንና የገበያ ኢኮኖሚን ማስፋፋት ይበጃችኋል” የሚለው የቻይና መንግስት ምክርም ጥሩ ነው፡፡ ኢህአዴግ ጥሩ ምክር ሲያጋጥመው መስማት አለበት፡፡ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ተቃዋሚዎችም በበኩላቸው ትንሽም ይሁን ትልቅ፣ ኢህአዴግ ጠቃሚ ምክሮችን አገናዝቦ እንዲቀበል ግፊት ማድረግ አለባቸው። የኢኮኖሚ ነፃነት አስተማማኝ የብልጽግና መንገድ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ውሎ አድሮ ለፖለቲካ ነፃነትም አጋዥ ይሆናል፡፡     

የዘንድሮ ምርጫ ለወሬ
አላመቸም (ለኢህአዴግም ለተቃዋሚም)

    በመንግስት ማዲያ በተደጋጋሚ ተነግሮናል “የህዝቡ የዲሞክራሲ ግንዛቤ እየዳበረ እንደመጣ በዘንድሮው ምርጫ ታይቷል”፡፡ እንዴት ነው የታየው?
ከተመዝጋቢ መራጮች መካከል፣ 93% ያህል ድምጽ ሰጥተዋል፡፡ ይህም ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለአለም ሁሉ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ተብሏል - በመንግስት ሚዲያ፡፡
“በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል” እንደሚባለው ሆኖ ነው እንጂ፤ ለካ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የአሜሪካና እንግሊዝን ስንትና ስንት ያስከነዳል፡፡
በእርግጥ በምርጫ ብዙ ድምጽ ሰጪ በማስቆጠር ትንሽ የሚበልጡን አገራት አሉ፣ እ…እነ ሶሪያና ኩባ…መሆናቸው ነው ችግሩ፡፡ በዚህ አቅጣጫ ምርጫውን እያደነቅን ብዙ ለማውራት ያስቸግራል አይደል? ለወሬ አይመችም፡፡
በርካታ ተቃዋሚዎች እንደሚያደርጉት ምርጫውን ከጫፍ እስከ ጫፍ ማጣጣልስ ያስኬዳል? እውነት ነው፤ የግል ሚዲያ ተዳክሟል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ እስርና ወከባ በርክቷል፡፡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ እና በዜጐች ኑሮ ውስጥ የመንግስት ድርሻና ቁጥጥር ተስፋፍቷል…   
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ነፃ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡ ነገር ግን፣ በርካታ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎች ሲናገሩት የነበረው ክስተት አልተፈጠረም።
የምርጫ ካርዳቸውን እየቀደዱ እንዲጥሉ ለመራጮች ቀርቦ የነበረው ጥሪ ማለቴ ነው፡፡ ከተመዝጋቢ መራጮች መካከል 93% ያህሉ ድምጽ ከሰጡ፣ የምርጫ ካርዱን ቀድዶ የጣለ ብዙ ሰው የለም ማለት ይቻላል፡፡ ባለፉት ምርጫዎችም ከዚህ የበለጠ መራጭ ድምጽ አልሰጠም - በመቶኛ ሲሰላ፡፡
ምናልባት አብዛኛው መራጭ ድምጽ የሰጠው በፍርሃት ስሜት ስለታፈነ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን እንዲሁ ስታስቡት፣ ያ ሁሉ ሰው በየምርጫ ጣቢያው የተሰለፈው በፍርሃት ተጐትቶ ነው? ያ ሁሉ ሰው “ነፃነት ወዳድ” ቢሆንም፣ ኢህአዴግን የማይፈልግ ቢሆንም፣ በፍርሃት ተገፋፍቶ ኢህአዴግን ይመርጣል? እውነት እንዲህ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ባህርይ ሙሉ ለሙሉና በቀላሉ በፍርሃት ስሜት የሚነዳ  ከሆነ፣ ይሄ አገር ተስፋ የለውም። ማለቴ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የዚህን ያህል በፍርሃት ስሜት አእምሮው ተቃውሶ የሚጃጃል ከሆነ‘ኮ፣ እዚህ አገር ደህና ሰው የለም ብንል ይሻላል፡፡ እሺ፤ በገጠር አካባቢዎችስ ይሁን…የመንግስት አፈናና ቁጥጥር ከከተሞች ይልቅ በገጠር ይብሳል፡፡ የከተማ ነዋሪዎች ለምሳሌ የአዲስ አበባና የባህርዳርና የአዳማ፣ የመቀሌና የድሬዳዋ፣ የአዋሳና የደሴ፣ የሃረርና የጐንደር ነዋሪዎች እንዴት በቀላሉ በፍርሃት ስር ይወድቃሉ? ጀብደኛ ይሁኑ ማለቴ አይደለም፡፡ ፍርሃት ጨርሶ አይንካቸው እያልኩም አይደለም፡፡ ብዙ ሰው ተቃውሞ ለማሰማት ቢፈራ አይገርምም፡፡ ስለዚህ መቃወም ይቅር፡፡ ግን ድምጽ ሳይሰጥ ቢቀር እገደላለሁ እታሰራለሁ ብሎ ይፈራል? የምርጫ ጣቢያ ሄዶ፣ የድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ ማንም ሳያየው ምልክት ማድረግስ አይቻልም?
ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለኢህአዴግ ድምጽ የሰጡት በእንዲህ አይነት ፍርሃት አእምሯቸው ተቃውሶ ማሰብ ስለተሳናቸው ነው የምንል ከሆነ፤ ነፃነትን የሚፈልግ ሰው ከአገሪቱ ጠፍቷል ብለን ብንደመድም ይሻላል፡፡ በቃ፤ አገሬው ተስፋ የለውም ማለት ነው፡፡
ይሄኛው አቅጣጫም ለወሬ አይመችም፡፡
እና ምን ተሻለ? እንደገና ወደ ኢህአዴግ አቅጣጫ ተመልሰን፤ “ህዝቡማ አዋቂ ነው፤ ዲሞክራሲ ገብቶታል፤ በአሜሪካና በእንግሊዝ 60 በመቶ ያህል መራጭ ነው ድምጽ የሚሰጠው፡፡ በኢትዮጵያ ግን 93% ሆኗል” ብለን እናጨብጭብ? በዚህ አቅጣጫ “ዲሞክራሲ” እያስፋፋን ከቀጠልን የት እንደምንደርስ አስቡት፡፡ ከኛ የሚበልጥ “ሪከርድ” ያስመዘገቡ አገራት ላይ እንደርሳለን፡፡ 95%...ከዚያም በላይ እስከ 99.9% እንሄዳለን፡፡
እንዲህ በአለም አቻ የሌለው የ “ዲሞክራሲ” ምጥቀት ያስመዘገቡ አገራት ሰሜን ኮሪያ፣ ኩባ፣ ሶሪያ…ኧረ ሩቅ መሄድ አያስፈልገኝም፡፡ ጐረቤታችን ሶማሊያም የዚህ ሪከርድ ባለቤት ነበረች፡፡
ምናለፋችሁ? እስከዛሬ ከአገራችን ፓርቲዎች የምንሰማቸው እንዲህ አይነት ነገሮች፣ ፍሬ አልባ አዙሪት ነው፡፡ ይልቅስ ቆም ብለን የአገራችን ችግር ምን እንደሆነ በቅጡ ብንመረምር ይሻላል፡፡ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የምርጫ ዘመቻ እያካሄዱ ያሉት ሴናተር ራንድ ፖል ሰሞኑን እንደተናገሩት፤ ስልጣኔንና ነፃነትን ነጣጥሎ ማየት አንዱ የፍሬ አልባ የአዙሪት ምንጭ ነው፡፡ ከኋላቀርነት ለመላቀቅ፣ ለአእምሮና ለሳይንስ፣ ለቢዝነስና ለነፃ ገበያ፣ በአጠቃላይ እያንዳንዱን ሰው እንዳሰራውና እንደ ድርጊቱ የምንመዝንበት ስልጡን ባህል ለማዳበር መራመድ ካልጀመርን በቀር፣ ነፃነት ብቻውን በአንዳች ተዓምር እውን ቢሆን እንኳ ውሎ አያድርም፡፡ በሌላ በኩልም የስልጣኔ ጅምር፣ ያለ ፖለቲካ ነፃነት ብዙ እድሜ አይኖረውም፡፡ በእንጭጩ ይጠወልጋል፡፡ በሌላ አነጋገር የአገራችን ሁኔታ ከነፃነት እጦት ብቻ ሳይሆን ከኋላቀርነትም የመነጨ ነው፡፡  

    ከ10 ዓመት በኋላ ደረጃውን የጠበቀ ዓለም አቀፍ ባንክ ለመሆን ወጥኖ እየተንቀሳቀሰ ነው - በፋይናንስ ኢንዱስትሪው በአገሪቷ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፡፡ ህልሙን ለማሳካት እየፈጸማቸው ከሚገኙት ተግባራት አንዱ ባለፈው ሳምንት መገናኛ አካባቢ ያስመረቀው ባለ 17 ፎቅ የልህቀት ማዕከል (ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ) ተጠቃሽ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በባላንስድ ስኮር ካርድ የእቅድ አወጣጥ ስልት ባደረገው የሀብት ማሰባሰብ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትግበራና በሰው ሀብት ልማት ስትራቴጂ አማካይነት አመርቂ
ውጤቶች ማስመዝገቡን በልህቀት ማዕከሉ ህንፃ ምረቃ ወቅት ፕሬዚዳንቱ አቶ በቃሉ ዘለቀ ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ከአምስት ዓመት በፊት በ2010 ከነበረው ብር 55 ቢሊዮን ተቀማጭ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ብር 223 ቢሊዮን፣ ከ220 ቅርንጫፎች ወደ 956፣ የደንበኞችን ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን ወደ 10.1 ሚሊዮን፣ ጠቅላላ ሀብቱ ደግሞ ከ74 ቢሊዮን ወደ 297 ቢሊዮን ብር ማደጉን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ባንኩ አሰራሩን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመለወጥ በየቅርንጫፎቹ በየቀኑ በአማካይ 700ሺህ የገንዘብ ልውውጦች እንደሚደረግ እንዲሁም በካርድ፣ በሞባይል ባንኪንግና በኢንተርኔት ባንኪንግ በየቀኑ በአማካይ ከ80ሺህ በላይ የገንዘብ ቅብብሎሽ እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡ በአምስት ዓመቱ እቅድ ወቅት የባንኩ አጠቃላይ ሰራተኞች ቁጥር 8,726 ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በብዙ እጥፍ ጨምሮ 22,475 መድረሱን ጠቅሰው፣ ይሄም ባንኩ ለሰው ሀብቱ ስትራቴጂ የሰጠውን ትኩረት ያመለክታል ብለዋል፡፡ ይህን ዕቅዱን የሚያስፈጽመው ደግሞ ብቻውን አይደለም፡፡
ከጀርመኑ ፍራንክፈርት ስኩል ኦፍ ፋይናንስ ኤንድ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ነው፡፡
ካለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ የሰው ኃይል ልማት ስትራቴጂን ከነማስፈጸሚያ ስልቱ ቀርፆ ሥራ ላይ በማዋሉ የተቀናጀ የአሰራር ስልት እንዲኖረው መደረጉ ታውቋል፡፡ በዚሁ መሰረት ባንኩ በዓለም ምርጥ (ወርልድ ክላስ) ንግድ ባንኮች የሚያከናውኑ ሰባት የስራ ዘርፎች፣ በዘመናዊ የሰው ኃይል ትራንዛክሽን፣ ኢምፕሎይመንት ኢንጌጅመንትና ኮሙኒኬሽን ካርየር ማኔጅመንትና  የኤች አር ቢዝነስ ፓርትነሪንግ ስራዎች በማዕከልም ሆነ በዲስትሪክት ጽ/ቤቶች እየተሰራበት እንደሆነ አቶ በቃሉ አመልክተዋል፡፡
አንድ ድርጅት የቱንም ያል በዘመናዊ መሳሪያዎች ቢደራጅ በራሱ አይንቀሳቀስም፡፡ የተማረ (የሰለጠነ)፣ የላቀ ችሎታና ከፍተኛ የሙያ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ይፈልጋል፡፡ በሰው ሀብት ልማት ስትራቴጂ ስልጠናው ከወትሮው የተለየ፣ ጥልቀት ያለው፣ ለለውጥና ለፈጠራ ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችል መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ለስልጠና ቦታዎች አመቺነትና ምቹነት ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
በዕለቱ የተመረቀው የልህቀት ማዕከልም ለዚህ የሰው ኃይል ልማት ስትራቴጂ ዋነኛ አጋዥ እንዲሆን ታቅዶ የተሰራ ነው፡፡ በምድር ቤቱ ካለው ቅርንጫፍ ባንክ በስተቀር ለሥልጠናና ተያያዥነት ላላቸው የአዕምሮ ማበልጸጊያ ተግባራት እንዲያመች ተደርጎ መሰራቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ የተመረቀው ህንፃ 17 ፎቆች ያሉት ሲሆን ሁለቱ ፎቆች ለመኪና ማቆሚያ የተመደቡ ናቸው፡፡ 1ኛው ፎቅ ለባንኩ ሰራተኞችና ባንኩን አገልግለው ጡረታ ለወጡ ሰራተኞች የጂምናዚየም ገልግሎት ይሰጣል፡፡ የህንፃው ምድር ቤትና መዳረሻ የተቀላጠፈ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በባንክ ኢንዱስትሪ ዕድገት ታሪክ ውስጥ ባበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ትልቅ ስፍራ በያዙትና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ በነበሩት (በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል)  በክቡር ዶ/ር ተፈራ ደግፌ ስም የተሰየመ ነው፡፡ የህንፃው 1ኛ ፎቅ ከጂምናዚየም በተጨማሪ ለሰልጣኞች የሬስቶራንት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ 2ኛው ፎቅ ቤተ-መፃህፍት ሲሆን ከ3ኛ እስከ 12ኛ ፎቅ ያሉት ክፍሎች የስልጠና አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ “ሕዳሴ” የሚል ስም የተሰጠው ህንፃው፤ አንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ የስልጠና ክፍሎች አሉት፡፡   

Saturday, 27 June 2015 08:35

ክረምት ወለድ በሽታዎች

በጉንፋን የተያዘን ሰው ከሚጨብጡት ቢስሙት ይሻላል

    የክረምቱን መግባት ተከትለው የሚከሰቱ እንደ ጉንፋን ያሉ የጤና ችግሮች ለበርካቶቻችን ጤና መጓደል ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነኚህ የጤና ችግሮች የአተነፋፈስ ስርዓትን የሚያውኩና ለከፋ የጤና ችግር የሚዳርጉን ሲሆኑ በክረምቱ ወራት መግቢያና መውጫ ላይ በስፋት የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በቫይረስ ሳቢያ ከሚከሰተው የጉንፋን በሽታ ጨምሮ፣ ፍሉ፣ የአፍንጫ አስም፣ ሳይነሣይተስ፣ የሳንባ አስም፣ የመተንፈሻ ቱቦዎች መታወክ፣ ሳንባ ምችና የዲያፍራሞች መዳከም የክረምቱን መግባት ተገን አድርገው የሚዘምቱብን የጤና ችግሮች ናቸው፡፡ ክረምት ወለድ በሽታዎች በአብዛኛው በቫይረሶች፣ በኢንፌክሽኖች፣ በባክቴሪያና ፈረሶች የሚከሰቱ
ሲሆኑ አንዳንድ ጊዜ በአለርጂ ሳቢያ ሊመጡ የሚችሉም ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ የክረምቱን ወራት መምጣት ተከትለው ከሚነሱና ብዙዎቻችንን ለጤና መጓደል ከሚዳርጉን ክረምት ወለድ በሽታዎች መካከል ጥቂቶቹን በማንሳት፣ ስለበሽታዎቹ ምንነት፣ ምልክቶቻቸው፣ ስለሚያስከትሉት የጤና ችግርና መፍትሄዎቻቸው ባለሙያ የሚለውን እናጋራችሁ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሀኪም የሆኑት ዶክተር አብርሃም ተስፋዬ፤ ክረምት ወለድ በሽታዎችን እንዲህ ይገልጿቸዋል፡፡ ከክረምት ወለድ በሽታዎች መካከል ጉንፋን፣ የአፍንጫ አስም፣ ሳይነሳይትስ አስም፣ ሃይፐርሊን፣ ሲቲቪቲ፣ ኒምናይትስ እና በአለርጂ ሳቢያ የሚከሰቱ የመተንፈሻ አካላት ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጉንፋን ከክረምት ወለድ በሽታዎች መካከል በስፋት የሚታወቀውና ለበርካቶች ጤና መጓደል ምክንያት የሚሆነው ዋንኛው ችግር የጉንፋን በሽታ ሲሆን ይህም በቫይረስ አማካይነት የሚከሰትና ከ280 በላይ ዓይነቶች ያሉት ነው፡፡ ጉንፋን ከአፍንጫ ጀምሮ ወደ ውስጥ ያሉትን የመተንፈሻ  አካላት የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ ለአብዛኛዎቹ የጉንፋን በሽታ ዓይነቶች መነሻ የሚሆነው
ራይኖቫይረስ የተባለው ቫይረስ ሲሆን ይህ ቫይረስ ከመተንፈሻ አካላት በተጨማሪ የጆሮና የብሮንካይ አካባቢዎችንም ያጠቃል። በጉንፋን በሽታ በምንያዝበት ወቅት ዐይናችን፣ ጆሮአችን፣ ጥርሳችንና ጉንጫችን ላይ የህመም ስሜት የሚኖረንም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ጉንፋን ከቀላል የኢንፍሊዌንዛ ህመም ጋር የሚመሳሰልበት ሁኔታ አለ፡፡ ከፍተኛ ራስ ምታት፣ ሳል፣ ማስነጠስና የምግብ ፍላጎት መቀነስ በሁለቱም በሽታዎች ላይ በስፋት የሚታዩ ምልክቶች ሲሆኑ ማስነጠስ፣ ንፍጥና ቀጭን የአፍንጫ ፈሳሽ፣ ዓይን እንባ ማቆር፣ አፍንጫን ውስጠኛ ክፍል ማሳከክ፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ መንቀጥቀጥ፣ በላብ መጠመቅና ትኩሳት በጉንፋን በሸታ ወቅት የሚታዩ ምልክቶች ናቸው፡፡ ከጉንፋን አምጪ  ቫይረሶች መካከል የአብዛኛዎቹ መተላለፊያ መንገድ ከትንፋሽ ይልቅ ንኪኪ ነው። እጅግ የተለመደው አስተላላፊ ንኪኪ ደግሞ በቫይረሱ የተበከለ እጅን በመጨበጥ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጉንፋን የተያዘው ሰው የነካቸውን ዕቃዎች መነካካትም ለበሽታው መተላለፊያ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ በጉንፋን የተያዘን ሰው ከመሳም ይልቅ መጨበጡ በሽታው በቀላሉ ወደጤናማው ሰው እንዲተላለፍ ያደርገዋል፡፡ ጉንፋን የያዘውን ሰው በሚጨብጡበት ወቅት የሚጨብጡት በአፍንጫ ፈሳሽ የራስ ናፕኪን  /መሃረብ/ ይዞበት የነበረውን እጁን ነው፡፡ ህመምተኛው ናፕኪን ወይም መሃረብ ካልያዘ ደግሞ አፍንጫውን ለማበስ በተደጋጋሚ እጆቹን ወደ አፍንጫው መላኩ አይቀሬ ነው፡፡ እርስዎ  ታዲያ ጉንፋን ከያዘው ወዳጅዎ ጉንፋኑ እንዳይጋባብዎ ሰግተው ወዳጅዎን ከመሳም ይልቅ መጨበጡ የተሻለ እንደሆነ አምነው፣ ይህንኑ ሲከውኑ በቫይረስ የተበከለው የወዳጅዎ እጆች ጉንፋን
አምጪ ቫይረሶችን ያቀብልዎታል ይህንኑ በቫይረሱ የተበከለ እጀዎን ከመታጠብዎ በፊት አፍንጫዎንና አይንዎን የሚነካኩበት አጋጣሚ ከተፈጠረ በቀላሉ በቫይረሱ ሊበከሉና ለጉንፋን በሽታ ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም በጉንፋን የተያዘን ሰው ከሚጨብጡት ይልቅ ቢስሙት የተሻለ ነው፡፡ የአፍንጫ አስም (ሪይናይቲስ)
በሳይንሳዊ አጠራሩ አለርጂክ (ሪይናይቲስ) የሚባለውና በተለምዶ የአፍንጫ አስም እያልን የምንጠራው ህመም በስፋት ከክረምት መምጣት ጋር ተያይዞ የሚከሰትና ክረምት ወለድ እየተባሉ ከሚጠሩ በሽታዎች መካከል የሚጠቀስ የጤና ችግር ነው፡፡ ይህ በሽታ የሚከሰተው ለአፍንጫ አካባቢ አለርጂክ በሚሆኑ ሽታዎች፣ ለምሳሌ፡- በዝናብ በራሰ አቧራ (የአፈር ሽታ) የዛፍና የተለያዩ ነገሮች ሽታዎች፣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያና የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ሽታ፣ የመኪና ጭስ ለበሽታው መከሰት ዋንኛ መንስኤ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ለአንድ ሰው አለርጂ የሚሆኑ ነገሮች በሌላው ሰው ላይ ችግር ላያስከትሉ ስለሚችሉ የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች አለርጂ የሆኑባቸውን ነገሮች ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በአፍንጫ አስም እና በጉንፋን መካከል ካሉት ልዩነቶች ዋንኞቹ የአፍንጫ አስም አለርጂ ቀስቃሽ ነገሩ ወደ አፍንጫችን እንደደረሰ ወዲያውኑ በደቂቃ ውስጥ ህመሙ የሚጀምር ሲሆን ጉንፋን በቫይረሱ ከተበከሉ ከቀናት በኋላ ህመሙ ይጀምራል፡፡ በጉንፋን ህመም ወቅት  የመገጣጠሚያ፣ የጀርባና የጡንቻ ህመሞች የሚከሰቱ ሲሆን በአፍንጫ አስም ላይ ግን እነዚህ ምልክቶች አይታዩም፡፡ ሳይነሳይተስ በፊት አጥንቶች አካባቢ በሚገኙና በአየር በተሞሉ ትናንሽ ቦታዎች ላይ የሚከሰት የህመም አይነት ሲሆን በተለምዶ ሳይነስ እየተባለ ይጠራል። በፊት አጥንቶች አካባቢ፣ በአፍንጫችን፣ በአፍንጫችን በስተጀርባ ያሉና በቆዳና በአጥንት ተሸፍነው በሚገኙ ውስጣቸው ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ ህመሙ ይከሰታል፡፡ ፎሮንታል፣ ማግዚለሪ፣ ኢሞማድ፣ አስፈኖይድ አና በቀኝና ግራ አፍንጫችን ላይ የሚገኙት እነዚህ ክፍት ቦታዎች በአደጋ፣ በአለርጂ፣ በኢንፌክሽንና በቲሞር አማካኝነት ችግር ሲገጥማቸው የሳይነስተስ በሽታ ይከሰታል፡፡ ከእነዚህ መካከል በስፋት የሚከሰተው በአለርጂ ምክንያት
የሚከሰተው ሳይነሳይተስ ነው፡፡ እነዚህ በፊት አጥንቶች አካባቢ የሚገኙትና በአየር የተሞሉት ትናንሽ ቦታዎች አለርጂ ቀስቃሽ በሆኑ ኢንፌክሽኖች በሚጠቁበት ጊዜ የክፍት ቦታዎቹ ሽፋን ያብጥና ወደ አፍንጫ የሚሄደው ቱቦ መሰል ቀዳዳ ይዘጋል፡፡ በዚህ ወቅትም ታማሚው ብርድ ብርድ የማለት ስሜት፣ የትኩሳት መኖር፣ እራስ ምታት፣ የአፍንጫ ማፈንና ማሳከክ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ በሽታው በተለይ ከአይን፣ ከጆሮ፣ ከጉሮሮ፣ ከሳምባና ከአንጎላችን ጋር ቁርኝት አለው፡፡ አንድ ሰው በዚህ በሽታ ቢያዝ እነዚህ የሰውነት ክፍሎችም ጥቃቱ ይደርስባቸዋል፡፡ የሳይነሳይትስ (ሳይነስ) በሽታ በተለይ በስኳር በኩላሊት፣ በቲቢና በኤድስ ህሙማን ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ በአገራችን በስፋት የሚታየውን የአለርጂ ሳይነሳይተን ለመከላከል አለርጂ
የሚሆኑባቸውን ነገሮች በጥልቀት በማጥናት ማስወገዱ፣ ዋንኛ መፍትሄ መሆኑን ባለሙያው
ይናገራሉ፡፡ የታችኛው የመተንፈሻ አካላት ህመሞች እነዚህ ህመሞች የታችኛውን የመተንፈሻ አካላት የሚያጠቁ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ኒሞኒያ፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ የሳንባ ውሃ መቋጠር የሳንባ ካንሰር፣ አጣዳፊ ብሮንካይትስና ኢንፍሎዌንዛ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ በታችኛው የመተንፈሻ አካላት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች ከላይኛው የመተንፈሻ አካላት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች በበለጠ አደገኛ ናቸው፡፡ በኢንፌክሽን ከሚመጡ ህመሞች ውስጥ ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋውን የሟቾች ቁጥር የያዙት በዚሁ በታችኛው የመተንፈሻ አካላት ላይ በሚፈጠር ህመም ሳቢያ የሚሞቱ ናቸው፡፡ በሽታው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና እጅግ አደገኛ የሆነ በሽታ መሆኑንም ዶክተር አብርሃም ገልፀዋል፡፡ የክረምትን መምጣት ተከትለው የሚከሰቱና በርካቶችን ለከፋ የጤና ችግር ከሚዳርጉ በሽታዎች ለመጠበቅ የራስንና የአካባቢን ንፅህና መጠበቅና አለርጂ ከሚሆኑ ነገሮች መጠንቀቅ ጠቃሚ እንደሆነም ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡   

Published in ዋናው ጤና
Page 3 of 16