Saturday, 27 June 2015 08:31

የፎሪ፣ የፎሪ…”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ስሙኝማ…ባል ሚስቱን… “እኔ ብሞት ሌላ ባል ታገቢያለሽ?” ሲል ይጠይቃታል፡፡ እሷም…
“በጭራሽ አላገባም፣” ትለዋለች፡፡
እሱም…
“ታዲያ ካላገባሽ ከማን ጋር ትኖሪያለሽ?” ሲል ይጠይቃታል፡፡ እሷም…
“ከእህቴ ጋር እኖራለሁ፣” ትላለች፡፡ አያይዛም… “አንተስ፣ እኔ ብሞት ሌላ ሚስት ታገባለህ!” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡ ምን ብሎ ቢመለስላት ጥሩ ነው…“በጭራሽ፣ እኔም ከእህትሽ ጋር እኖራለሁ፡፡”
ልፊ ሲላት አንድ እንጨት አስራ አረፈች፡፡እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ነገርዬዋን ከነቢይ ላይ የተዋስኳት ነች፡፡ የሸገር የጨዋታ እንግዳ ላይ ከመዓዛ ጋር ሲጨዋወቱ የጥንት የስፖርት አስተማሪውን ትውስታ ሲያወራ የተናገራት ነች። የሆነ ጨዋታ ላይ አንዱ የቡድናቸው ተጫዋች ኳሷን እየገፋና እያታለለ ይገሰግሳል፡፡ አሰልጣኝም በሜዳው ጠርዝ እኩል እየሮጠ ያበረታታዋል፡፡ ታዲያላችሁ… ተጫዋች ሆዬ ከዳር ዳር ኳሷን ይዞ ሄዶ ጎል አጠገብ ይደርስና ኳሷን ይቀመስልሽ ይላታል፡፡ ኳስ ሆዬ ወደ ውጪ! ይሄኔ እኩል ሲሮጥ የነበረው አሰልጣኝ ይበሽቅና ተጫዋቹን በስም ጠርቶ ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“የፎሪ፣ የፎሪ ቅድም አታወጣውም ነበር!” ምን ያድርግ…ትንፋሹን አስጨርሶት ጉድ ሲያደርገው!
እናማ….እኛም ትንፋሻችን እያለቀ ጉድ እየሆንን ዘንድሮ ‘የፎሪ፣ የፎሪ…’ የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉን፡፡
እግረ መንገዴን…ሚስት ትንሽ ሲደባብራት ትከርማለች፡፡ እናላችሁ…ወደ ሀኪም ዘንድ ሄዳ ትመለሳለች፡፡ ባልም…
“ዶክተሩ ምን አለሽ?” ይላታል፡፡ እሷም…
“አንድ ወር በባህር ዳርቻ፣ ሁለት ሳምንት በገጠር ነፋሻ ስፍራ፣ አንድ ሳምንት ደግሞ ከአገር ውጪ እንዳሳለፍ መከረኝ፣” ትለዋለች፡፡ ባልም አጉረምርሞ ዝም ይላል፡፡ ሚስትም…
“እሺ ውዴ፣ መጀመሪያ ወዴት ነው የምትወስደኝ?” ትለዋለች፡፡ ምን ቢላት ጥሩ ነው…
“ወደ ሌላ ዶክተር…”
ልፊ ሲላት አንድ እንጨት አስራ አረፈች!
እናላችሁ…“የፎሪ፣ የፎሪ…” የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉን፡፡ የሆነ መሥሪያ ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራል፡፡ ሠራተኛውም ስለ መቶ አንድ ችግሮቹ አለቆቹን ወጥሮ ሊይዝ “ይለያል ዘንድሮ…”
ምናምን እያለ ቀኑን ይጠብቃል፡፡ ታዲያላችሁ…በስብሰባው ቀን ጠዋት ምን ይሆናል… ‘አጣዳፊ
በሆነ ሥራ ምክንያት የዛሬው ስብሰባ ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል’ የሚል ማስታወቂያ ይለጠፋል፡፡ አንድ ሳምንት ሙሉ ሲያምጥ የኖረ ሠራተኛ ሁላ እጢው ዱብ ይልላችኋል፡፡“የፎሪ፣ የፎሪ…” ማን ስብሰባ ጥሩ አላቸው! ነገርዬው እኮ… “ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል፣” አይነት ነው፡፡
የሆነች እንትናዬ በ‘አዲስ ጓደኝነት’ ትመጣለች። እናላችሁ…ማኪያቶ፣ ብላክ ፎረስት ኬክ፣ ቺዝ በርገር፣ ክትፎ ምናምን ስትጋበዝ ትከርማለች፡፡ አጅሬው ደግሞ…አለ አይደል… “ሁሉም ሙሉ፣ ሁሉ ዝግጁ” ይልና የ‘እነሆ በረከት’ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ይሄኔ እሷዬዋ…“እኔ’ኮ ሌላ ሰው አለኝ፣” ትለዋለች፡፡ ምን! ሌላ ሰው ብሎ ነገር ምንድነው? ያ ሁሉ ቺዝ በርገርስ!… ያ ሁሉ ብላክ ፎረስት ኬክስ!... የዮሐንስ ክትፎስ!
ታዲያ “የፎሪ፣ የፎሪ…” መጀመሪያ የብላክ ፎረስት ኬኩ ጊዜ ሰው አለኝ አትልም ነበር!
ነገርዬው እኮ… “ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል፣” አይነት ነው፡፡እናማ…‘የፎሪ፣ የፎሪ…’ የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉን፡፡ ‘ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ ለመላው ሠራተኛ የሁለት ደረጃ የደሞዝ እድገት ይሰጣል’ ይባልና ሠራተኛ ሆዬ ቢጠብቅ ምንም፣ ቢጠብቅ ምንም፡፡ ታዲያላችሁ… ወደ መጋቢት አካባቢ አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራና…“ድርጅቱ የበጀት እጥረት ስለገጠመው የደሞዝ እድገቱ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል…” ይባላል፡፡ ሠራተኛው እኮ ገና ለገና ገንዘብ
አገኛለሁ ብሎ ስንት ነገር በዱቤ ወስዷል!
‘የፎሪ፣ የፎሪ…’ መጀመሪያውኑ ማን ቃል ገቡ አላቸው፡፡ነገርዬው እኮ… “ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል፣” አይነት ነው፡፡ስሙኝማ…እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሚስት ባሏን ምን ትለዋለች…
“ጋዜጣ በሆንኩ ብዬ እመኛለሁ፡፡” ባልም…
“ለምን?” ይላታል፡፡ እሷም…
“ምክንያቱም ቀኑን ሙሉ ይዘኸኝ ትውል ነበር፣” ትለዋለች፡፡ ባልም…
“እኔም ጋዜጣ ብትሆኚ ብዬ እመኛለሁ፣” ይላታል፡፡ እሷም…
“ለምን?” ትለዋለች፡፡ ምን ብሎ ቢመልስላት ጥሩ ነው…
“ምክንያቱም በየቀኑ አዳዲስ ጋዜጣ እይዛለሁ…” ብሏት አረፈ፡፡ ካላጣችው ማመሳከሪያ ማን በጋዜጣ
‘ተቀኚ’ አላት!
እናላችሁ “የፎሪ፣ የፎሪ…” የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉ፡፡‘ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል’ ተብሎ ይለጠፋል፡፡ እናላችሁ… እኛም “እስቲ እንሞክረው...” ብለን እንገባለን፡፡ ሹሮ ሆዬ እንኳን ልትሻሻል ብሶባት አብሲት ነገር ሆና ትመጣለች፡፡ ቂ…ቂ…ቂ….
ሀሳብ አለን… አንዳንድ ምግብ ቤቶች ከሹሮ አብሲቱ ጋር ትንሿን ምጣድ አብራችሁ አቅረቡልንማ!
አሀ…አንደኛውን ጋግረን የሹሮ እንጀራን በጤፍ እንጀራ እያጣበቅን እንበላለና!
እናማ… “የፎሪ፣ የፎሪ…” መጀመሪያውኑ ማን… “ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል…” ቅብጥርስዮ በሉ
አላቸው!
እግረ መንገዴን…አንዱ ምን አለ መሰላችሁ…“ወንዶች ‘ቅድሚያ ለሴቶች’ ብለው ሴቶችን ፊት ፊት የሚያስቀድሙት ለትህትና ሳይሆን መቀመጫቸውን ለማየት ነው” አለ አሉ፡፡ እንዴት፣ እንዴት አድርጎ ቢያስበው ነው! ነገርዬውማ፣
መቼስ ለምን ይዋሻል… አለ አይደል….እውነቱን ለመናገር እንኳ ‘ፊት፣ ፊታችን’ ሆኖልን አንገታችንን
መቶ ሰማንያ ዲግሪ እየጠመዘዝን ‘እሱኑ’ ስንገረምም አይደል እንዴ የምንውለው! ይሄ ‘ጂም’
የሚሉት ነገር ‘ከቦታው እያጠፋው’ አስቸገረን እንጂ!  ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ…“የፎሪ፣ የፎሪ…” የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉ፡፡
ደግሞላችሁ…የእኔ ቢጤ ‘ጠሀፊ’ ነገር… “ምን የመሰለ አዲስ አሪፍ መጽሐፍ አውጥቻለሁና አንበቡልኝ…” ምናምን ነገር ሲደሰኩር ይከርማል፡፡ ከዛም አንባቢ እየሸመተ ማንበብ፡ ቢያነብ፣ ቢያነብ የተባለውን “አሪፍ…” ምናምን ነገር አያገኝም፣ ባዶ ይሆንበታል፡፡ (‘እንደ በፊቶቹ መጽሐፍት... ማለት ይቻላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…) ከዛማ የተበሳጨ አንባቢ... “ምን አለ በተወደደ ወረቀት ባይጫወቱበት... ምናምን አይነት አስተያየት ሲበዛ የኔ ቢጤው ‘ፉዞ’ ነገር ሆኖ ቁጭ ይልላችኋል፡፡ አሀ… መጀመሪያውኑ “የፎሪ፣ የፎሪ…”… አለ አይደል… “አሪፍ መጽሐፍ…” ምናምን ማን በሉ አለን!እናማ…“የፎሪ፣ የፎሪ…” የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉ፡፡ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ ባሏን ‘ይማግጣል’ ብላ ትጠረጥረዋለች፡፡ ትሄድና ሽጉጥ ትገዛለች።
በማግስቱ ባሏን ከምትጠራጠራት ሴት ጋር እጅ ከፍንጅ (‘መርፌና ክር’ ሆነው…) ትይዛቸዋለች። ሽጉጧን ታወጣና ራሷ ግንባር ላይ ትደግናለች፡፡ ይሄን ጊዜ ባሏ ራሷን እንዳትገድል ይለምናታል፡፡ እሷ ምን ብትለው ጥሩ ነው…“ዝም በል፣ ከሀዲ! የእኔን ጨርሼ ወደ አንተ ነው የምዞረው!” ከሞኝ እንትናዬ ይሰውራችሁማ፡፡
“የፎሪ፣ የፎሪ…” ማን ሽጉጥ ግዢ አላት! ቂ…ቂ…ቂ…
ይቺን ስሙኝማ…ሚስት ባሏን…
“ከመጋባታችን በፊት ስንት የሴት ጓደኞች ነበሩህ?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡ባል ዝም ብሎ ይቀመጣል፡፡ እሷም… “ምን ይዘጋሀል፣ ንገረኝ እንጂ!” ስትል ትጮህበታለች፡፡ እሱ ምን ይላል… “ረጋ በይ፣ ገና እየቆጠርኩ ነው፡፡ አ…አሥራ አራት፣ አሥራ አምስት…” ሲል እሷዬዋ ታብዳለች አይገልጻትም፡፡ “ማን ቁጠርልኝ አለህ!  ማን ስለ ሴት ጓደኞችህ አውራልኝ አለህ!” ምናምን እያለች ቤቱን ታምሰዋለች፡፡ አሀ…“የፎሪ፣ የፎሪ…” ማን “የሴት ጓደኞችህ…” ምናምን ብላ ነገር ቀስቅሺ አላት!እኔ የምለው…እንትና ተጠቃለልክ እንዴ! የምር ለካስ… “ውሽማ ሲቆይ ባል ይሆናል፣” የሚባለው እውነት ነውና!በገባህበት እግርህ ደግመህ እንዳትወጣና… “የፎሪ፣ የፎሪ…” አስብለህ እንዳታስተርተንማ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…እናማ… “የፎሪ፣ የፎሪ…” የሚያሰኙን ነገሮች በዝተዋል፡፡
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Published in ባህል

“የአቶ አንዳርጋቸው አያያዝ የአገራቱን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው”
- የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሊፕ ሃሞንድ

   የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚገኙበት ሁኔታና አያያዛቸው፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ ለኢትዮጵያ መንግስት ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
አቶ አንዳርጋቸው የቆንስላ ድጋፍ ማግኘት በማይችሉበት ወይም ይግባኝ የመጠየቅ መብት ባላገኙበት ሁኔታ በግልጽ በማይታወቅ ስፍራ ከሰው ተነጥለው ለብቻቸው መታሰራቸውን ያወገዙት ውጭ ጉዳይ ሚነስትሩ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በግለሰቡ ጉዳይ ላይ አፋጣኝ ማሻሻል እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ ባለፈው ረቡዕ ከኢትዮጵያው አቻቸው ከዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ዙሪያ በስልክ ባደረጉት ውይይት፣ ግለሰቡ እስሩን በህግ ለመቃዎም ዕድል ባላገኙበት ሁኔታ ከሰው ተነጥለው ላለፈው አንድ አመት በእስር ላይ መቆየታቸው ያሳስበኛል ብለዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸውን በየጊዜው ለመጎብኘት የምንችልበት ሁኔታ እንዲመቻችልን ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል ከመግባት ባሻገር ተገቢ ምላሽ ሊሰጠን አለመቻሉ አሳዝኖኛል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ አለመስጠቱ ተቀባይነት የለውም፣ በግለሰቡ ጉዳይ ዙሪያ ይህ ነው የሚባል መሻሻል አለመታየቱም ትልቅ ስፍራ የምንሰጠውን የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ ለዶ/ር ቴዎድሮስ መናገራቸውንም ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ለቤተሰባቸው የሚያደርገውን
የቆንስላ ድጋፍ ለወደፊትም እንደሚቀጥል ሃሞንድ ተናግረዋል፡፡የአቶ አንዳርጋቸው ጠበቃ ቤን ኩፐር በበኩላቸው፤ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግለሰቡ ከሰው ተነጥለው መታሰራቸውንና መጎብኘት እንዳለባቸው በማረጋገጥ እስሩን መቃወሙ አስደስቶናል፣ ይሄም ሆኖ የእንግሊዝ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ተለቀው ወደ እንግሊዝ በመመለስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ እንዲያመቻችልን እንጠይቃለን ማለታቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የተመድ የስቃይ ጉዳዮች ምርመራ ልዩ ባለሙያ ጁዋን ሜንዴዝ በበኩላቸው፤ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን አያያዝ በተመለከተ ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ
ለሁለቱም አገራት መንግስታት ማስታወቃቸውን ጋዜጣው ጠቁሟል፡፡

Published in ዜና

“የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ስለዲሞክራሲ የተሳሳተ መልዕክት ያስተላልፋል”
 
   የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቀጣዩ ሐምሌ ወር ኢትዮጵያን ይጐበኛሉ መባሉን ተከትሎ ታላላቅ አለማቀፍ ሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቸ ተቋማት ተቃውሞአቸውን እየገለፁ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ፕሬዚዳንቱን እንዲመጡ የሚያደርጋቸው የአገራችን የውስጥ ስኬት ነው ሲል ተቃውሞውን አጣጥሎታል፡፡ የኦባማ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን ርዕሰ ጉዳያቸው ካደረጉ የአሜሪካ ሚዲያዎች አንዱ የሆነው ዘ ዋሽንግተን ፖስት በርዕሰ አንቀፁ ባሰፈረው ተቃውሞ፤ “የኦባማ ኢትዮጵያን መጐብኘት
ስለዲሞክራሲ የተሳሳተ መልዕክት ያስተላልፋል” ብሏል፡፡ በእንግሊዝ ከፍተኛ ተሰሚነትና ተነባቢነት ያለው ዘ ጋርዲያንም ጉብኝቱን አስመልክቶ በርዕሰ አንቀፁ ባሰፈረው ሃተታ፤ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ዲሞክራሲያዊ ላልሆኑ ስርአቶች እውቅና መስጠት ነው ሲል ክፉኛ ተችቷል፡፡ ኦባማ ጋናን በጎበኙበት ወቅት፤ “መጀመሪያ የምንደግፈው የተጠናከረ ዲሞክራሲያዊ መንግስትን ነው” በሚል የተናገሩትን ዘንግተውታል ያለው ዋሽንግተን ፖስት፤ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ኢትዮጵያን የመሳሰሉ በሰብአዊ መብት ረገጣ ለሚታሙ ሃገራት እውቅናና ከለላ መስጠት ነው ሲል ተቃውሟል፡፡ “በቅርቡ ሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ የመንግስት ሽግግር ያደረገችው ናይጄሪያን የመሳሰሉ በዲሞክራሲ ጐዳና ላይ እየተጓዙ ላሉ ሀገራት እውቅና መንፈግ ነው” ሲልም የታቀደውን የኢትዮጵያ ጉብኝት ጋዜጣው አብጠልጥሎታል፡፡ ጉብኝቱ ኢትዮጵያና አሜሪካ ያላቸውን የዘመናት ግንኙነት እንዲሁም ሃገሪቱ በቀጠናው ያላት የፀጥታ አስከባሪነት ሚናና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገቷን ታሳቢ ያደረገ ነው መባሉን ያስታወሰው ዋሽንግተን ፖስት፤ የሀገሪቱ መንግስት በዚያው ልክ ነፃ ሚዲያ የማያበረታታ እንደውም ያሉትንም እያጠፋና የፖለቲካ ጫናዎች እያሳደረ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሶ ጉብኝቱን ተቃውሟል፡፡
ባለፈው ዓመት ከሰኔ ወር ጀምሮ 34 ጋዜጠኞች ከሀገር እንዲሰደዱ መደረጋቸውን ጋዜጣው ጠቁሞ፣ ሃገሪቱ ጋዜጠኛ አሳሪ በመባል ከሚታወቁ የአለም ሀገራት በቀዳሚነት መሰለፏን ጠቅሶ የኦባማን ጉብኝት ተችቷል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዊንዲ ሸጋርማን በቅርቡ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት “ኢትዮጵያ ዲሞክራሲዋን እያጠናከረች ነው፣ የምታከናውነው ምርጫም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው” የሚል ምስክርነታቸውን በሰጡ ማግስት፣ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የምርጫ ውጤቱን ከ99.6 በመቶ ወደ መቶ በመቶ ማሳደጉ፣ ዲሞክራሲውን ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል ሲል ነቅቷል ዋሽንግተን ፖስት፡፡በዘንድሮ ምርጫ ተቃዋሚዎች እንግልትና እስራት እንደተፈፀመባቸው፣ አለማቀፍ ታዛቢዎች ምርጫውን እንዳይታዘቡ መከልከላቸውን፣ በምርጫው ማግስትም ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ የነበሩ ፖለቲከኛ እንደተገደሉ የጠቀሰው ጋዜጣው፤ ሆኖም መንግስት ስለተገደሉት ሰዎች ኃላፊነት አልወሰደም ብሏል፡፡ የተረጋጋ፣ ሰላማዊና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ያካሄደችው ናይጄሪያ እያለች ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ለለውጥ ላልተዘጋጀው የኢትዮጵያ መንግስትና ለአሳፋሪው
የምርጫ ውጤት እውቅና መስጠት ነው ያለው ዋሽንግተን ፖስት፤ ለአፍሪካውያንም ዲሞክራሲ ጠቃሚ አይደለም የሚል መልዕክት ያስተላልፋል ሲል ጉብኝቱን አጥብቆ ተቃውሟል፡፡ ታዋቂው የእንግሊዝ ጋዜጣ ዘ ጋርዲያን በበኩሉ፤ የኦባማ ኢትዮጵያን መጎብኘት ለጨቋኝ መንግስት ስጦታ ነው ሲል ፅፏል፡፡ “ሃገሪቱ በኢኮኖሚ እያደገች ቢሆንም በዜጎች ሰብአዊ መብት አያያዝና በፕሬስ ነፃነት እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ በኩል ተወቃሽ ነች፣ የዲሞክራሲ ተምሳሌት ልትሆንም አትችልም” ብሏል ጋዜጣው በርዕሰ አንቀፁ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም የፕሬዚዳንቱን የኢትዮጵያ
ጉብኝት አበክረው ተቃውመዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ምርጫ በአፈና ስር ያለ የፖለቲካ ልምምድ ነው”
ያለው ‹ፍሪደም ሃውስ› የተሰኘ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ቡድን፤ የኦባማ ጉብኝት ለፖለቲካና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መቀጨጭ አጋርነትን ማሳየት ነው ሲል በመግለጫው ተችቷል፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ አንዳንድ ወገኖች የኦባማን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እየተቃወሙ መሆኑን እንደሚያውቁ ጠቁመው፤ ፕሬዚዳንቱን እንዲመጡ የሚያደርገው የሀገራችን የውስጥ ስኬት ነው ብለዋል፡፡
“የኦባማ መምጣት ትልቅ ትርጉም አለው” ያሉት አቶ ሬድዋን፤ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን ለመጐብኘት
የማቀዳቸው ሚስጥር የኢኮኖሚ እድገቱ እንዲሁም ሀገሪቱ ለሠላም እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ ስኬታማና አይነ ግቡ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ “በ112 አመታት የዲፕሎማሲ ታሪክ የአሜሪካ 44ኛው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን መጐብኘት ትልቅ የገጽታ ግንባታ ይኖረዋል፤ ቤታችን መጽዳትና መሞቅ መጀመሩንም ያረጋግጣል” ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

Published in ዜና

ህብረተሰቡ ለ10 ቀናት በእቅዱ ላይ ይወያያል ተብሏል

    መንግሥት የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መቶ በመቶ አለማሳካቱን ገልፆ ለ5 ዓመት በሚዘልቀው በሁለተኛው የእቅድ ዘመኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አንደሚወያይና ተጨማሪ እቅዶችንም በማከል ዕቅዱን እንደሚያሳካ አስታውቋል፡፡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ትናንት በፅ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት በየክልሉና በፌደራል ደረጃ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ጠንካራ ውይይት ይደረጋል ብለዋል፡፡ “በእቅዱ ላይ መንግስት በፌደራል ደረጃ ሁሉንም የሃገሪቱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ያወያያል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ በያንዳንዱ መድረክ እስከ 600 የሚደርሱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጣይ 5 ዓመት በሚተገበረው የመንግስት የልማት እቅድ ላይ ይመክራሉ ብለዋል፡፡ የደቡብ፣ የኦሮሚያ፣ የአማራና ጋምቤላ ክልል መንግስታት በጉዳዩ ላይ ዛሬና ነገ ከህብረተሰቡ ጋር የሚወያዩ ሲሆን የአዲስ አበባ ሰኞ እና ማክሰኞ ይሆናል ተብሏል፡፡ በፌደራል ደረጃ በሚካሄደው ውይይት የሲቪክ ማህበራት፣ የግል ባለሀብቶች እና የተለያዩ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ይሳተፋሉ፤ ለእቅዱም ግብአት ያመነጫሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አውስተዋል፡፡
ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን የኢኮኖሚ ሽግግር ማቀላጠፍ ዋነኛው የሁለተኛው ዘመን እቅድ የመንግስት ግብ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዓመታዊ ሀገራዊ እድገት (GDP) ላይ ግብርናው አሁን ያለው 40 በመቶ ድርሻ ወደ 36 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጎ፣ ኢንዱስትሪው አሁን ካለበት 14 በመቶ ወደ ላይ ከፍ እንዲል ይደረጋል ብለዋል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው 5 በመቶ ድርሻ ወደ 8 በመቶ ማሳደግም ዋነኛው እቅድ ነው ተብሏል፡፡ በሃይል ልማቱም የህዳሴ ግድብ ግንባታን ማቀላጠፍ ጨምሮ የተለያዩ የኃይል ምንጮችን በመገንባት ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በሁለተኛው የእቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ አመርታለሁ ብሏል - መንግስት፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት ሲተገበር የነበረው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በአጠቃላይ ተለጥጦ የተዘጋጀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግስት ሙሉ ለሙሉ ማሳካት አለመቻሉን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በተለይ በስኳር ልማት፣ ባቡር መስመር ግንባታና የወረዳ - ቀበሌ መንገድ ግንባታዎች ከእቅዱ በታች የሆነ አፈፃፀም ተመዝግቦባቸዋል ብለዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክትና ከጅቡቲው የባቡር መስመር በተጨማሪ ሌሎች እንዳይተገበሩ ዋነኛው እንቅፋት የገንዘብ እጥረት መሆኑ ተጠቁሟል። እያንዳንዱን የገጠር ቀበሌ ከወረዳ የሚያገናኙ 71ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ለመስራት ታቅዶ 40 ሺህ ያህሉ መሰራቱን ያወሱት ሚኒስትሩ፤ ለእቅዱ ሙሉ ለሙሉ አለመሳካት የሎጀስቲክና የሰለጠነ
ሰው ኃይል እጥረት ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ “ግብርናውም 8 በመቶ እንደሚያድግ ታስቦ የነበረ ሲሆን በአማካይ 6.6 በመቶ አድጓል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ አፈፃፀሙ መልካም ነው ብለዋል፡፡ በአጠቃላይም በመጀመሪያው የእቅድ ዘመን ያልተሳኩት የሁለተኛው የእቅድ ዘመን አካል ሆነው ይጠናቀቃሉ ብለዋል፡፡ ለቀጣይ እቅዱ ማስፈፀሚያ የሃገር ውስጥ ቁጠባን ከማሳደግ የሚገኝ ገቢ አንዱ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በመጀመሪያው  የእቅድ ዘመን ወደ ምርት ገብተው ለሁለተኛው እቅድ ገቢ ያመነጫሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ሁሉም የስኳር ፕሮጀክቶች ምርት ባለመጀመራቸው ሃገሪቱ አገኛለሁ ብላ አስባ የነበረውን በዓመት 600 ሚሊዮን ዶላር (12 ቢሊዮን ገደማ) ማጣቷን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱን አጠናቆ የተጠቀሰውን ያህል ገቢ ማመንጨትም የሁለተኛው እቅድ አካል ይሆናል ተብሏል፡፡

Published in ዜና

“ድርጊቱን የፈፀሙት በውጭ አገር የሚገኙ ግለሰቦች ናቸው” - ት/ቤቱ

     ከቢ አካዳሚ በተባለ የአፀደ ህፃናትና ህፃናት ማቆያ ት/ቤት ልጆቻቸውን እየከፈሉ የሚያስተምሩ ወላጆች፤ “እኛ ሳናውቅ ልጆቻችን በድረ ገፅ መለመኛ ተደርገውብናል” ሲሉ ያማረሩ ሲሆን ት/ቤቱ በበኩሉ፤ ድርጊቱን የፈፀሙት በውጭ ሀገር የሚገኙ ግለሰቦች ናቸው ብሏል፡፡ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 02/03 የሚገኘው ከቢ አካዳሚ፣ የልጆቻችንን ፎቶግራፎች በድረገፆች እየተለጠፈ የእርዳታ ማሰባሰቢያና መለመኛ አድርጐብናል ያሉት ወላጆች፤ ራሳቸውም መለመኛ ከመሆን እንዳላመለጡ ይናገራሉ፡፡ “እኛም አልቀረልንም፤ የአንዳንድ ወላጆች ፎቶግራፍም ለመለመኛነት ውሏል” ብለዋል፡፡ ት/ቤቱ አፀደ ህፃናትን ጨምሮ የህፃናት ማቆያ (ዴይኬር) አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በአፀደ ህፃናት ለሚማሩ ልጆቻቸው በወር 500 ብር፣ በማቆያ ለሚገለገሉ ህፃናት ደግሞ በወር 600 ብር እንደሚከፍሉ ወላጆች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ “በልጆቻችን ላይ የተፈፀመው ድርጊት በእጅጉ የስነ ልቦና ጉዳት አድርሶብናል” ያሉት የወላጅ
ተወካዮቹ፤ ጉዳዩን ካወቁ በኋላ ለህግ አካላት ቢያመለክቱም ቀና ምላሽ ሳያገኙ መቆየታቸውን ጠቁመው ባለፈው ረቡዕ ለክፍለ ከተማው አስተዳደር ማመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ የክፍለ ከተማው አስተዳደርም ጉዳዩ በወረዳ 2 በኩል እንዲታይ ወስኖ፣ በትናንትናው እለት ወረዳው ለፍትህ ቢሮ ክስ ማቅረቡን የወላጅ ተወካዮች ገልፀዋል፡፡ ወላጆቹ ባሰባሰቧቸው የድረ - ገፅ መረጃዎች ላይ የህፃናቱ ፎቶግራፍ ከሙሉ የማንነት መግለጫ ጋር ተቀምጦ፣ በትይዩ ለትምህርት ፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉና እርዳታ እንዲለግሱ
ጐብኚዎችን የሚጠይቅ የተማፅኖ መልዕክት ሰፍሯል፡፡ Kobiacademy.org በሚለው ድረ ገጽ ላይም ተማሪዎች በህብረት የተነሷቸው እንዲሁም የወላጆች መምህራንና የተማሪዎች የተናጠል ፎቶግራፎች መለጠፋቸውን ጠቁመው በእንግሊዝኛ “Donate Now!” (አሁን ይርዱ) የሚል መልዕክት መቀመጡን ወላጆች ገልፀዋል፡፡
የአፀደ ህፃናት ተማሪ የሆነች ልጅ ያላቸው አቶ መላ የተባሉ ወላጅ፤ የልጃቸው ፎቶግራፍ በተናጠል ከአጭር የማንነት መግለጫና የእርዳታ ጥያቄ ጋር በድረገፁ መቀመጡን ጠቁመው የራሳቸውም ፎቶግራፍ “ከወላጆች አንዱ፤ አቶ መላ ገ/ሚካኤል” ከሚል መግለጫ ጋር ተለጥፏል፡፡በድረገፁ ላይ አካዳሚው በአሜሪካ የተደራጀ ኮሚቴ እንዳለው መጠቆሙንና የኮሚቴው ተግባርም ስትራቴጂክ እቅድና ግብ መንደፍ እንዲሁም፤ የምክርና የእርዳታ ማሰባሰብ ስራዎችን እንደሚሠራ ተገልጿል ብለዋል - ወላጆች፡፡ በኮሚቴው ውስጥም ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ግለሰቦች እንዳሉበት በፎቶግራፍ ከተደገፉ የማንነት መግለጫዎች ተረድተናል ያሉት ወላጆች፤ ኮሚቴው በዋናነት የእርዳታ ማሰባሰብ ስራ እንደሚሠራ መጠቀሱንም ይገልፃሉ፡፡
ጉዳዩን የሰሙት ከወር በፊት ከት/ቤቱ አካባቢ መሆኑን የጠቆሙት ሌላዋ ወላጅ ወ/ሮ ፍቅርተ፤ መረጃውን ከሰሙ በኋላ ለተወሰኑ ወላጆች በመጠቆም፣ በጋራ ሆነው የት/ቤቱን አስተዳደር ቢያነጋግሩም አስተዳደሩ ቀና ምላሽ እንዳልሠጣቸው ያስረዳሉ፡፡ ከቀናት በኋላ ግን አስተዳደሩ ወላጆችን ስብሰባ ጠርቶ “ልጆቻችን መለመኛ ሆኑ የምትሉ ወላጆች ኮሚቴ ምረጡና ትከሳላችሁ” ብለዋቸው አራት አባላት ያሉት የወላጆች ኮሚቴ መዋቀሩን ይገልፃሉ። ኮሚቴውም ተሰብስቦ ለመክሰስ የሚያስችለውን ቃለ ጉባኤ በሚያረቅበት ወቅት የት/ቤቱ አስተዳዳሪ
አቶ ሚካኤል፤ “እኛ ሳናውቅ ውጭ ያሉ ሰዎች የፈፀሙት ድርጊት ነው፤ እኔም ከእናንተ ጋር ከሳሽ ነኝ” ማለታቸውን የኮሚቴው አባላት ይናገራሉ፡፡ የድርጅቱ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል ተክሌ ስለጉዳዩ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ “ድርጊቱ የተፈፀመው ከዚህ አይደለም፤ ውጭ ሀገር ካለው ጋር የተያያዘ ነው፤ ከኛ ጋር አይገናኝም፤ ስለጉዳዩ እንደማናውቅም በማስረጃ አስደግፈን ለወረዳው አመልክተናል” ብለዋል፡፡  

Published in ዜና

 ህጋዊ መታወቂያ ወይም የጉዞ ሰነድ አልያዙም ተብሏል
- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአ/አ ስንነሳ ህጋዊ ሰነድ ነበራቸው ብሏል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአየርላንድ ርዕሰ መዲና ደብሊን በኩል ወደ አሜሪካ ሎሳንጀለስ የጀመረውን አዲስ በረራ ለማስመረቅ ባለፈው ቅዳሜ ከአዲስ አበባ በመነሳት ባደረገው ጉዞ፣ ተሳታፊ የነበሩ 7 ኢትዮጵያውያን መንገደኞች፣ አውሮፕላኑ ደብሊን አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ሲያርፍ ወደ ኢሚግሬሽን ክፍሉ አምርተው ጥገኝነት መጠየቃቸውን አይሪሽ ኢንዲፔንደንት ትናንት ዘገበ፡፡ሁለት ህጻናትን ጨምሮ ጥገኝነት የጠየቁት 7 መንገደኞች በአየር ማረፊያ ጣቢያው ሲደርሱ ምንም አይነት መታወቂያ ወይም የጉዞ ሰነዶችን አልያዙም ነበር ያለው ዘገባው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቃል አቀባይ ግን፣ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች በሙሉ ከአዲስ አበባ ሲነሱ ህጋዊ ሰነዶችን ይዘው ነበር፣ ስለ ጥገኝነት ጠያቂዎቹ የግል ጉዳይ ግን አስተያየት መስጠት አንፈልግም ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ ላለፉት ከ40 በላይ አመታት ወደ አውሮፓ አገራት በረራ ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት ቃል አቀባይዋ፣ የምናጓጉዘው የተሟላ ህጋዊ የጉዞ ሰነድና ተገቢ ቪዛ ያላቸውን መንገደኞች ብቻ ነው ሲሉ መናገራቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡አንድ የአገሪቱ የህግ ክፍል ቃል አቀባይም የተለያዩ አገራት መንገደኞች በደብሊን አየር ማረፊያ ጣቢያ ሲደርሱ ጥገኝነት መጠየቃቸው የተለመደ የዘወትር ክስተት ነው፣ ባለፈው አመት ብቻ 221 መንገደኞች ለትራንዚት አርፈው ጥገኝነት ጠይቀዋል ብለዋል፡፡

Published in ዜና

   ሰሞኑን ‹‹የዳኛቸው ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ ያሳተምኩትን መጽሀፍ ተከትሎ በየቦታው አቧራ ተነስቶ ከርሟል፡፡ በርካቶችም የአቧራውን ጭስ ብቻ በመከተል ተቧድነዋል፡፡ እኔም እውነታው ብዙ ነገር ስለሚያናጋ ይህንን ጽሁፍ እስከምጽፍበት ጊዜ ድረስ አተካራ ውስጥ ላለመግባት ሞክሬያለሁ። በሌላ በኩል ከእውነታውና ከምጠብቀው ፍጹም የተቃረነ ነገር ስለገጠመኝ መደናገጤን መሸሸግ አይቻለኝም። ለዶክተር ዳኛቸው የነበረኝ አክብሮት፣ ያልተፈተሸ ፍቅር ብሎም አሁን ያሉበት ሁኔታም መልስ ከመስጠት እንድቆጠብ ካደረጉኝ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዝምታዬ አንዳንድ ሰዎችን ወደ ገደል ሲመራም አስተውያለሁ፡፡ ከዶክተር ዳኛቸው ጋርም አሁን ባለበት ሁኔታ በንግግር መግባባት አልቻልንም፡፡ በመሆኑም ነገሩ የህልውና ጉዳይ እየሆነና በሚያስደነግጥ ሁኔታ መልኩን እየቀየረ ስለመጣ በአቧራው ጭስ የተሸፈነውን እውነት
ለመገላለጥና ለተሰነዘሩብኝ እጅግ ሰቅጣጭ ውንጀላዎች መልስ ለመስጠት እግረ መንገዴንም በአንባቢዎቼ ላይ የተጋረዱትን ብዥታዎች ለማጥራት ስል ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ተገድጃለሁ፡፡ዛሬ ላይ ለውዝግብ የተዳረገው መጽሀፌን አስመልክቶ በግልጽ ከተናገርኩኝ አንድ ዓመት ከስድስት ወር አለፈው፡፡ ረቡዕ ታህሳስ 16 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣችው “ኢትዮ-ምህዳር” ጋዜጣ ላይ ‹‹በዳኛቸው ላይ የተሰነዘረ መርህ አልባ ትችት›› በሚለው ጽሁፌ ውስጥ በሚከተለው መልኩ ነበር የስራዬን መጠናቀቅ የገለጽኩት፡- ‹‹... ዶ/ር ዳኛቸው ተነቦ የማያልቅ መጽሀፍ ነው፣ በሀሳቦቹ ውስጥም የኢትዮጵያን ችግሮች ማየትና መመርመር ይቻላል፣ ታሪክንም ሆነ ፍልስፍናን ጠንቅቆ ያውቃል፣... በግል ተነሳሽነት ሀሳቦቹን መርምሬ በመጽሀፍ መልክ እያዘጋጀኋቸው እገኛለሁ፡፡ ሌላው ወገን ደግሞ ከፈለገ ተቃራኒውን ሀሳብ አንስቶ በምክንያት መሞገት ይችላል፡፡... ›› ከላይ
የጠቀስኩት ጽሁፍ ለህትመት በበቃበት ቀን የዕለቱ ጽሁፌን ዶ/ር ዳኛቸውን ጨምሮ በዙሪያው የነበሩ ፕሮፌሰሮችና ወዳጆቹ በጣም እንደወደዱትና ከመጽሀፌ ጋር በተያያዘ ይፋ ያደረግሁት ነገርም እንዳስደሰታቸው ዳኛቸው እራሱ በደስታ ስሜት ውስጥ እንዳለ ነበር ደውሎ የነገረኝ፡፡ በወቅቱ እኔ ከአዲስ አበባ ውጪ ስለነበርኩ በተደጋጋሚ የተገናኘነው በስልክ ነበር፡፡ ጽሁፉንም በኢሜል እንድልክለት ጠይቆኝ ልኬለታለሁ፡፡ በቅርቡም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረረ በኋላ ለኢሳት ሰጥቶት የነበረውን ቃለ መጠይቅ እንዳስደምጠው በጠየቀኝ መሰረት፤ ይዤለት እቤቱ ሄድኩና ተገናኘን፡፡ ፕሮግራሙንም ይዤለት የሄድኩት በኮምፒውተሬ ነበር። ሰምቶ እንደጨረሰም እዛው በተቀመጥንበት ከኮምፒውተሩ ላይ ለህትመት ዝግጁ የሆነውን ስራ በጋራ እያሳለፍንና እያወራንበት አየነው፡፡ አይቶ እንደጨረሰም ካልተሳሳትኩኝ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነ ወዳጁ ጋር ይደውልና እጅግ በተገረመ ስሜት ውስጥ ሆኖ ‹‹ስማ እንጂ... ያ ጉደኛ ልጅ አንዴት አድርጎ መሰለህ መጽሀፉን የሰራው! ... የሚገርም ነው መቼም እልሀለው፤ ስንገናኝ አወራሀለሁ....›› ነበር ያለው፡፡ እነዚህን ሁለት ማሳያዎች ዳኛቸው ከመጽሀፌ መውጣት ጋር ተያይዞ ከሰጠው ሀሳብ ጋር አነጻጽሩት፡፡ እነዚህን ነጥቦች የማነሳቸው ዳኛቸው ለሰጠው አስተያየትም ሆነ አብዛኞቻችሁ ለምታነሱት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥልኝ እንጂ እኔ በግሌ የዳኛቸው ሀሳቦች ላይ ትንታኔም ሆነ ትችት ለመስራት የግዴታ እሱ ማየትና መፍቀድ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ብዙዎች መጽሀፉን ሳያነቡ ከድምዳሜ
ላይ እንደደረሱት መጽሀፉ የእሱ ሃሳቦች ስብስብ ሳይሆን በዳኛቸው ሀሳቦች ላይ ትንታኔ የሚያቀርብ
ነው፡፡ ይህንንም ዘግየት ብዬ በአስረጂ ማሳያ እመለስበታለሁ፡፡መጽሀፉ ገበያ ላይ ሊውል አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስም አንድም ተቃውሞ ከዶክተሩ ተቀብዬ አላውቅም፡፡ መጽሀፉ ሊወጣ አንድ ቀን ሲቀረው ዳኛቸው ጋ ሁኔታውን ልነግረው ስደውል ደሴ መሆኑን ነገረኝ፡፡ እኔም የመጽሀፉ ህትመት መጠናቀቁን ላበስረው እንደደወልኩኝ ስገልጽለት፤ ‹‹ልጅ መሐመድ ባለፈው ሳምንት የቀጠርኩህ እኮ በጉዳዩ ላይ እንድናወራ ነበር፤... ፐብሊሸሬ ኮንሰርን አለው፤ ብናወራ ጥሩ ነበር፤...›› ካለኝ በኋላ በነጋታው እንደሚመለስ ገለጸልኝ፡፡ እኔም መጽሀፉን እቤት ይዤለት እንደምመጣ ከተነጋገርን በኋላ በሰላም ተለያየን፡፡ በነጋታውም ዶክተር ደወለና ‹‹ ፐብሊሸሬ ኮንሰርን አለው፤ ደጋግሞ እየደወለልኝ ነው ›› ሲል ከሌላው ጊዜ ጠንከር ባለ ድምጸት አወራኝ፡፡ እኔም በዚህ ስራ ላይ የሱ አሳታሚን የሚያሳስበው ነገር እንደሌለ ስገልጽለት፣ ‹‹እንዴት
ነው የማይመለከተው፤ የኔን ስብስብ እኮ ላሳትመው ነው›› ሲለኝ ‹‹እና ምን ችግር አለው? የኔ ስብስብ ስራ አይደል፤ አንተ አታውቀውም እንዴ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ነው እንዴ! ስብስብ ነው ብለውኝ እኮ ነው›› ብሎ ሲለኝ እንደዛ በማሰቡና ሌሎችን በማመኑ ቅሬታዬን ገልጬለት ስልኩ ተዘጋ፡፡ ልብ አድርጉ! እንግዲህ እዚህ ሀገር ጠልፎ የሚጥለው ብዛቱ! መጽሀፉ ገና እኔ እጅ እንኳን ሳይገባ ስብስብ ስራ ነው እያሉ የሚያወሩ ነበሩ፡፡ መጽሀፉ እንደወጣም እቤቱ ሄጄ አስቀምጬለት ወጣሁ፡፡ መጽሀፉን ወደቤት ተመልሶ ገና ሳያገኘው አሁን የምንሰማውን ቅሬታ በዛኑ ዕለት ማታ መሰማት ጀመረ፡፡ ስለብቃቴ፣ መጽሀፌ መዉጣት፣... ያወደሱ አንደበቶች ወደዘለፋ ለመቀየር ጊዜና ማስተዋል አላስፈለጋቸውም፡፡ መጽሀፉን ሳያነቡ ወቀሳውን የሚያስተጋቡት ሌሎችም ነበሩ፡፡ ከዓመት በፊት የታወጀን እውነታ ካለማንበብ የተነሳ አለማወቅ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ አሁንም መጽሀፉን ሳያነቡ በቲፎዞነት የተሰለፉ በርካቶች ነበሩ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ በማስተዋል ውስጥ ሆናችሁ እኔንም ሆነ ሌሎችን ለማረጋጋት አስተውሎቱ የነበራችሁ ጥቂት የፌስቡክ መንደር ታዳሚዎች የምር ክብር ይገባችኋል፡፡ በቲፎዞነት ዓለም ውስጥ ለዋተታችሁ አብዛኞች ደግሞ ማስተዋልና ልቦናን ከክብር ጋር
ተመኘሁ!የጠሉትን መውረስ!ዳኛቸው አጥብቆ የሚነቅፋቸውን የስርዓቱ ተግባራት ለመፈጸም ጊዜ አልፈጀበትም። በኔው ስራ እኔኑ ከመጠየቅ ይልቅ ምርጫው ያደረገው ጀርባዬን ማጥናት ነበር፡፡ የጠላቸውንና የጠረጠራቸውን ሁሉ ከኔ ጋር ያጣብቃቸዋል፡፡ በውል እንኳን ከነመፈጠራቸው የማላውቃቸውን ሰዎች ስም እየጠራ ከጀርባህ እነከሌ ስላሉ እውነቱን አውጣ ማለቱን ተያያዘው፡፡ ከመጽሀፌ ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው
ውዝግብ ዋነኛ ማጠንጠኛውም ይሄው ነጥብ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶችም ለክብራቸው በማይመጥን መልኩ መሰሉን የመሸታ ቤት ሀሜት ሰምተው፣ በአደባባይ የግለሰቦችን ክብር የሚነካና በወንጀልም ጭምር ሊያስጠይቃቸው የሚችል ጽሁፍ ጽፈዋል፡፡ የዚህ ከጀርባዬ የሌለን ሰው የመፈለጉ ሽኩቻ በግላዊ ፀብ፣ በፖለቲካዊ ጥንስስ፣ በማፊያዎቹ ኣሳታሚዎች ፍላጎት፣... ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ እርግጠኛ ስላልሆንኩኝ ከጀርባ ስላለው ነገር አላወራም። የምፈልገው እከሌን እንጂ አንተን አይደለም፣ እናም መስክር፣ ... አይነት የፍረጃ ተግባሮች ሲተቹ የኖሩትን ስርዓት መንገድ መከተል ይመስላል፡፡ አስራት አብርሀምን እንኳን ካወቅሁት አንድ ወር አይሞላኝም፤ ግንኙነታችንም እሱ በሚካፈልበት ኤግቢሽን ላይ መጽሀፎቼን ለአንባቢም ሆነ ለነጋዴዎች እንዲሸጥልኝ ከማድረግ የዘለለ አይደለም፡፡ ሌላው ከነመፈጠራቸው የማላውቃቸው ሰዎች ስም እየተጠራልኝ ‹‹ከኋላህ አሉ!.. እራስህን ነጻ አውጣ... ሞኝ አትሁን...›› ዓይነት ማስፈራሪያ አዘል ንግግሮችም በጣም አስገራሚ ነበሩ። ከዚህም በላይ ለመጥቀስ የማይመቹ ዝርዝር ጉዳዮች እየተነሱ በማላውቀውና በማልጠብቀው አሳዛኝ ጉዳይ ውስጥም ተዘፍቄ ነው የከረምኩት፡፡ አስራትም ሆነ የሚጠሩልኝ ሰዎች የዶክተሩ እንጂ የኔ ወዳጆች አይደሉም፡፡ ከላይ ካነሳሁት ተግባር ጋር የሚመሳሰለው ዶክተሩ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ‹‹መሐመድ ይቅርታ ጠይቆኛል...›› በሚል ያነሱት ነጥብ ነው፡፡ ዶክተሩን ወደ አደባባይ ያወጣቸውና ተቀባይነትም ያስገኘላቸው ከብርቱካን እስር ጋር ተያይዞ ይህንን የይቅርታ ጠይቆኛል አባዜ፣ በከፍተኛ ሁኔታ
ማውገዛቸውና ጠንካራ አስተያየትም ማቅረባቸው ነበር፡፡ ከሰሞኑ ግን ዶክተሩ ይህንኑ ተግባር እንደልጄ አይሀለው በሚሉኝ እኔ ላይ በከፍተኛ ጭካኔ ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ መመስገንና መሸለም ሲገባኝ በከፍተኛ ሁኔታ የሞራል ኪሳራ የሚያደርሱ ጽሁፎችና ወሬዎች ሲያናፍሱ ከቆዩና በኋላም ክስ መስርተው ሲያበቁ በወጉ እንኳን ባልተስማማንበት የአንድ ቀን ግንኙነት ይቅርታ ጠይቆኛል አሉ፡፡ እኔ ዶክተሩን አስቀይሜ ይቅርታ ብጠይቃቸው እንኳን ካለን ቀረቤታ አንጻር እሳቸውን ደረት አስነፍቶ በአደባባይ የሚያስፎክር፣ የኔንም አንገት የሚያስደፋ አይደለም። የነበረውን ሁኔታ በግልጽ ላስቀምጠው፡፡ እኔና ዳኛቸው ከውዝግቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል የተገናኘነው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ስድስት ኪሎ አካባቢ ካለ አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ነበር፡፡
ግንኙነታችንም ከሳቸው በተነሳ ጥያቄ መሰረት ሚስጥራዊ እንዲሆን ብንስማማም በወቅቱ ያነሳናቸውን ጉዳዮች በተዛባ መንገድ እያነሱ ዛሬም ድረስ በስልክ የሚረብሹኝ ሰዎች አሉ፡፡ በወቅቱ ስንገናኝ የነበረው ሁኔታ ሚዲያው ላይ በሚራገበው መጠን ብዙም ውጥረት የበዛበት አልነበረም፡፡ በሂደት ሁለታችንም በሚያግባባን አንድ ነጥብ ላይ ማውራት ስላልቻልን ስሜቴ መረበሹ አልቀረም፡፡ ሆኖም ግን የምናወራው እንደ አባትና ልጅ ነበር፡፡ በኋላም በደረሰብኝ ነገር ሁሉ ስሜቴ ክፉኛ እንደተጎዳ፣ አስካሁን ከደረሰብኝ ጉዳት የባሰ ነገር በክሱም ቢሆን እንደማይገጥመኝ፣ ስራውንም ለገንዘብ ብዬ እንዳልሰራሁት፣ ወዘተ ካስረዳሁ በኋላ በዶክተሩ ፍላጎት እንዲወሰኑ ሁለት አማራጮችን አቀረብኩኝ። የመጀመሪያው አማራጭ እስካሁን የተበተነው መጽሀፍ የተበደርኩትንና መጽሀፉን ያሳተምኩበትን ወጪ ብቻ ከሸፈነ ቀሪዎቹን መጽሀፎች እንዲሰበሰቡ የሚል ሲሆን፤
ሁለተኛው አማራጭ መጽሀፉን ደግሞ የማሳተም ፍላጎት እንደሌለኝና አሁን የታተመው ግን ከኛ ቁጥጥርም ጭምር ዉጪ በመሆኑ ተሸጦ እንዳለቀ ለኔ የሚደርሰኝን ገንዘብ አምጥቼ ለዶክተር ልሰጥና፣ እሳቸውም በገንዘቡ ላይ የፈለጉትን ውሳኔ እንዲያሳልፉ የሚል ነበር፡፡ ይህንን በልመና ጭምር የታገዘውን አማራጭ ሳቀርብ አሁን የተፈጠረው አተካራ ማናችንንም እንደማይጠቅመን በማስረዳት ጭምር ነበር፡፡ በዚህ ላይ ለመወሰንም ለአርብ ጠዋት ቀጠሮ ይዘን ተሰነባበትን፡፡ የነበረው ነገር ይህ ነው፡፡ ገና ባልተቋጨ ጉዳይ ላይ ነው እንግዲህ “ይቅርታ ጠየቀኝ” በሚል መግለጫ የሰጡት። ታዲያ የቀጠሯችን ቀን አርብ ሲመጣ ከሳቸው በስልክ የደረሰኝ ውሳኔ ሳይሆን ቀደም ብዬ ከላይ ያነሳሁት የተጠናከረ ፍረጃ ነበር፡፡ ሌላውን ለማጥቃት እኔን መግደልም እንዴት
ምክንያታዊ እንደሚሆን አልገባኝም። እውነታውን በማስረጃ ለሚዲያው ፍጆታም ሆነ ሽያጭ ከኔ ይልቅ የዳኛቸው ፊት ገጽ ላይ መውጣት ሚዛን እንደሚደፋ እርግጥ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ከሰንደቅ ውጪ የትኛውም ሚዲያ ዘገባውን ሲሰራ ወደኔ በመደወል እውነታውን ለማጣራት ያልሞከረው፡፡ ባለፈው ሳምንት በወጣው የአዲስ አድማስ ዜና ላይም ዶክተር ዳኛቸው የመጽሀፉ 95 ከመቶ የሚሆነው ሀሳብ ከሳቸው እንደተወሰደ ተናግረዋል፡፡ የሆነው ሆኖ አንባቢ በእውነታው መካከል ያለውን ልዩነት አይቶ፣ የራሱን ፍርድ ይስጥ፤ እኔ ግን እውነታውን በቁጥር አስደግፌ ላስፈር፡፡ መጽሀፌ 236 ገጾች አሉት፡፡ በነዚህ ገጾች ውስጥ የዶክተሩ ሀሳቦች አስፈላጊ በሆኑበት ቦታ ላይ በሩብ፣ በግማሽ እና በሙሉ ገጽ ላይ እንደወረዱ የሰፈሩባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህ እንደወረዱ የተጠቀምኳቸው የዶክተሩ ሀሳቦች ተደማምረው ወደ 76 ያህል ገጽ ናቸው፡፡ ልብ አድርጉ 236 ገጽ ካለው መጽሀፍ ውስጥ 76 ገጽ ምን ያህል ፐርሰንት እንደሚሆን አስቡት፤ ወደ 32 ከመቶ ገደማ ነው፡፡ ከዚህ በቀጥታ የዶክተሩን ሀሳብ እንደወረደ ካሰፈርኩበት 76 ገጽ ውስጥ ደግሞ ወደ 30 ያህል ገጽ የሚሆነው ከኔው ጋር የቃለምልልስ ቆይታ በነበራቸው ወቅት የሰጡኝ ሀሳብ ነው፡፡ በተቀረው ገጽ ላይ የሰፈሩት ሀሳቦች የኔው ትንታኔዎች፣ ማብራሪያዎች እና አቶ ጌታቸውን ጨምሮ የሌሎች ሰዎች አጋዥ ስራዎች ናቸው፡፡ ይህንን ቁጥር እሳቸው ካሉት 95 ከመቶ ጋር ማነጻጸር ነው እንግዲህ፡፡ ይህንኑ እውነታ በሌላ ተጨባጭ ማስረጃ ለማስቀመጥ ያህል ሌላ ማሳያ ላምጣ፡፡ በመጽሀፉ እስከ 27ኛው ገጽ ድረስ የሳቸውን ሀሳብ እንደወረደ የተጠቀምኩት ሁለት ቦታ ላይ ከራሴው ጋር ካደረጉት ቆይታ ውስጥ ነው፡፡ ሽፋኑም ተደምሮ በገጽ ሲገመት አንድ ገጽ ከግማሽ ነው፡፡ ... ከገጽ 30 እስከ 35 ድረስ አንድ ቦታ ላይ ሩብ ገጽ ያህል ከ “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት” ላይ በቀጥታ ተወስዶ የሰፈረ ሀሳብ አለ፡፡... እንዲህ አድርገን ስንደምረውና በተለይም ከብርቱካን ጋር በተያያዘ የጻፉት ጽሁፍ፣ ለሰራሁት ትንታኔ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አብዛኛው ክፍል በመግባቱም ጭምር ነው ከላይ የጠቀስኩትን ያህል ቁጥር የመጣው፡፡ በመጨረሻም ከአንደኛው ገጽ ያልዘለለ ንባብና በስማ በለው በቲፎዞነት መሰለፍ ውጤቱን አደገኛ ያደርገዋል፡፡ መጽሀፉን ማንበብ ብቻ ወደትክክለኛው መንገድ ደርሰናል፡፡ አንብቦ ስራው አይረባም ማለት ይቻላል፡፡ ድምዳሜውን ለአንባቢያኑ መተው ይሻላል፡: በተረፈ ግን በቀሪ አተካራዎች ላይ ገብቶ መዋጀቱ ትንሹ እድሜዬ ሳይሆን በልበሙሉነት
የምናገርለት የሞራል ልዕልናዬ አይፈቅድልኝም፡፡ እውነቱ ይህ ነው! ትዕግስትም፣ ዝምታም፣
አክብሮትም ልክ አለው!!

- የፊሊፒንሳውያንን ያህል አሜሪካን የሚወድ የለም
- አሜሪካን በመጥላት የዮርዳኖስ ህዝቦች ይመራሉ

አሜሪካን በተመለከተ ያላቸውን አመላካት ለመለካከት ታስቦ በ39 የተለያዩ የዓለማችን አገራት ላይ የተሰራ አንድ ጥናት፣ ኢትዮጵያውያን አሜሪካን በመውደድ 3ኛ ደረጃ እንደያዙ መረጋገጡን ዘ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገበ፡፡ፒው ሪሰርች ሴንተር የተባለው የምርምር ተቋም በሰራው በዚህ ጥናት፣ አሜሪካን አጥብቀው
በመውደድ ቀዳሚዎቹ የፊሊፒንስ ዜጎች ሲሆኑ፣ ጋናውያንና ኢትዮጵያውያን ይከተላሉ ብሏል፡፡በጥናቱ ከተካተቱ ፊሊፒንሳውያን መካከል 85 በመቶው አሜሪካን እንደሚወዱ ሲናገሩ፣ በጋና 83 በመቶ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ 75 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለአሜሪካ ፍቅር እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡አሜሪካን በመውደድ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ህዝቦች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ የጠቆመው ጥናቱ፣ አብዛኞቹ የአውሮፓ፣ የእስያና የላቲን አሜሪካ አገራት ህዝቦችም ለአሜሪካ በጎ አመለካከት እንዳላቸው ማረጋገጡን ጠቁሟል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ አሜሪካን በመጥላት የዮርዳኖስ ህዝቦች ቀዳሚ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በጥናቱ ከተካተቱ የአገሪቱ ዜጎች 83 በመቶ ያህሉ አሜሪካን እንደማይወዱ ተናግረዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አሜሪካን የሚጠሉት ደግሞ ሩስያውያን ሲሆኑ በተለይ  ከቅርብ አመታት ወዲህ አሜሪካን የሚጠሉ ሩስያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ጥናቱ አረጋግጧል፡፡

Published in ዜና

ከአይሁዳውያን ተረት ውስጥ እንዲህ የሚል ይገኝበታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ብቸኛ ጫማ ሰፊ በአንድ ከተማ ይኖር ነበር፡፡ የዚያ ጫማ
ሰፊ አንድ ደንበኛ ጫማ ሊያሰራ መጥቶ ሳለ፤
“ጫማዬን በትክክል አልሰፋህልኝምና አልከፍልህም” ይለዋል፡፡
ጫማ ሰፊውም፣
“ከዚህ በላይ ልሰፋልህ አልችልም፡፡ የሰፋሁልህን ያህል ልትከፍለኝ ይገባሃል” አለው፡፡
“አልከፍልም”
“ትከፍላለህ!”
ግብ ግብ ገጠሙ፡፡ ጫማ ሰፊው ደምበኛውን በመዶሻ አናቱን ብሎ ገደለው፡፡
ተይዞ እከተማው ዳኛ ፊት ቀረበ፡፡
የከተማው ዳኛም፤
“ደምበኛህን ሆነ ብለህ በመዶሻ መትተህ በመግደልህ ሞት ይገባሃል፡፡ ይኸውም ሞት
በስቅላት መልክ የሚፈፀም ይሆናል፡፡” ሲሉ ፈረዱ፡፡ ፍርዱ ባደባባይ ተነበበ፡፡ ፍርዱን
ከሚያዳምጠው ህዝብ መካከል አንድ ሰው ተነስቶ፤
“የተከበሩ ዳኛ! እነሆ በከተማችን አለን የምንለውን አንድ ጫማ ሰፊ እንዲገደል
ፈርደዋል፡፡ ሆኖም ያለን ብቸኛ ጫማ ሰፊ እሱ ስለሆነ ከእንግዲህ ማን ጫማችንን
ይሰራልናል? ለህዝቡ ሊታሰብለት ይገባል!”
ሲል ሀሳብ አቀረበ፡፡ ሌሎችም ሰዎች በተራ በተራ እየተነሱ፤
“አስተያየት ይደረግልን”
“አስተያየት ይደረግልን”
“ያለን እሱ ብቻ‘ኮ ነው ምን ይውጠናል?” አሉ፡፡
የህዝቡ ሁኔታ የከተማው ዳኛ ሀሳባቸውን እንደገና እንዲያጤኑ አደረጋቸውና፤
“የከተማችን ህዝብ ሆይ በሀሳባችሁ እስማማለሁ፡፡ ያላችሁትም ዕውነት ነው፡፡ አንድ
ልብስ ሰፊ ቢኖረን እሱኑ መግደል ትክክል አይሆንም፡፡ በከተማችን ሁለት ጣራ ሰሪዎች
ናቸው ያሉት፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ አንደኛው እንዲሞት ወስኛለሁ! ፍርዱ በስቅላት የሚፈፀም
ይሆናል!” ሲሉ ፈረዱ፡፡
* * *
አንዱን አድን ብሎ አንዱን ከሚያስገድል፣ በፍርደ - ገምድልነት ከመፍረድና በህዝብ
ከመገፋት ይሰውረን! በትናንሽ ጠብ - ያለሽ በዳቦ ከመናቆርም ያድነና፡፡ የፍርድ ሂደት
በቲፎዞና በግፊት ከሆነ የህግ መንፈስ ጨርሶ ጥያቄ ውስጥ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ ህግ
ስነ-ሥርዓት አክብሮ የሚኖር ዜጋ ወገናዊነትንና ፍርደ - ገምድልነትን መቃወሙ ያለ፣
የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡
“ለመቶ አምሣ ጌታ
ስታጠቅ ስፈታ
ነጠላዬ - አለቀ በላዬ”፤ ያለችው ጭሰኛ ይሄንኑ የፍትህ መዛባትና የጌታ - የሎሌ ግንኙነት
አባዜ ስትግልጥ፣ ብሶቷንም ስታሰማ ነው፡፡ ዜጋ ቅሬታውንና በደሉን ማሰማቱ፣ ምንም
ቢዘገይ፣ አይቀርምና የፍትሕ አካላት ለሚያዛቡት ማናቸውም ፍርድ ተጠያቂነታቸው
አሌ አይባልም፡፡
በየትኛውም ሥርዓት ውስጥ ሥልጣን ላይ የሚቀመጡ ሹማምንት ከየት እንደመጡ፣
የት እንዳሉና ወዴት እንደሚሄዱ የዘነጉ ዕለት የጥፋት ህይወታቸው ይጀምራል፡፡ የበለጠው
ጥፋታቸው ደግሞ ጥፋታቸውን አለማመናቸው ነው፡፡ ከዚያ ቀጣዩ ደግሞ የአብዬን ወደ
ዕምዬ ማላከካቸው ነው፡-
ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የሚዋረዱት በሚሰሩዋቸው ስህተቶች
አይደለም፡፡ ይልቁንም፤ ስህተቶቻቸውን በሚይዙበት መንገድ
ምክንያት ነው” ይለናል ሮበርት ግሪን፡፡ (The way they deal with
their mistakes እንዲል)
“የአብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክ” የሚለው አባባል፣ Scapegoat የሚሉት በእንግሊዝኛ
መሰረታዊ - አመጣጡ በዕብራውያን ምክንያት ነው ይባላል፡፡ ይኸውም ለተሰራ ጥፋት
የፍየል መስዋዕት በማድረግ አገራቸውን ለማዳን ይሞክሩ በነበረበት ዘመን ነው፡፡ ከዚያም
ቢሆን ይሰውረን የዲሞክራሲ ጠር ነውና! ዲሞክራሲ እንደየአገሩ ፈሊጡም፣ አካሄዱም
እንደሚለያይ ማስተዋል ዋና ቁም ነገር ነው፡፡
ፋሪድ ዘካሪያ እንዲህ ይለናል፡-
… የበለጠ “ዲሞክራሲ” አለ በሚባልበት በአሜሪካ ሥርዓት ከዚህ
ቀደሙ የበለጠ ሥርዓተ - ነገሥታት (dynasties) አይተናል፡፡ የተከበሩ
ሹማምንት አይተናል፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተዳከሙ
ሲሄዱ፤ ሀብታም መሆን እና/ ወይም ዝነኛ መሆን፤ ለከፍተኛ ተመራጭ
ሹማምንት ተራ፣ የአዘቦት ጉዳይ ይሆናል፡፡
እኛ ሀገርም ከፊውዳሊዝም አብራክ ወጥቶ፣ በሶሻሊዝም አቋርጦ፣ አሁን ከካፒታሊዝም
ጋር በመፈጣጠም፣ እንውለደው እያልን የምናማምጠው ዲሞክራሲ፣ ከሌላ ከማናቸውም
አገር የተለየ ቢሆን አይገርምም፡፡ ተዋንያኑ አዋላጆች ግን ዛሬም እኛ ነን፡፡ የእኛ ማንነት
ደግሞ ንጥረ ነገሩ አንድ ነው፡፡ ታሪካችን፣ ባህላችን፣ ፖለቲካችን መሰረቱ አንድ ነው፡፡
ድንገት በአንድ ጀንበር አይለወጥም - “ከእትብት ጋር የወጣ አመል፣ ከከፈን ጋር ይቀበራል”
የሚባለው ተረት ዕውነት የሚሆነው ለዚህ ነው

Published in ርዕሰ አንቀፅ

 ለ11 ዓይነት በሽታዎች ፍቱን መድሃኒት አለኝ ይላሉ
     በዕፅዋትና የባህል መድሃኒት ዘርፍ ለ25 ዓመታት ምርምር አድርገዋል
     ከጫት ወይን የሚሰራበትን መንገድ በምርምር ማግኘታቸውን ይናገራሉ
           ለዓመታት በተማሩበትና በሰለጠኑበት የማህፀንና ፅንስ ህክምና ሙያ በተለያዩ የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች ረዘም ላለ ጊዜያት አገልግለዋል፡፡ ከዘመናዊው የህክምና ሙያ ጐን ለጐን በባህላዊ መድሃኒትና በዕፅዋት ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶችንና ጽሑፎችን ይከታተሉ ነበር፡፡ በመከታተል ብቻ ግን አልተገደቡም፡፡ ከ25 ዓመታት በላይ በዕፅዋት ምርምር ላይ መስራታቸውንም ይናገራሉ፡፡ በምርመራቸውም ከአስራ አንድ ለሚበልጡ የተለያዩ ህመሞች ፈዋሽ የባህል መድሃኒቶችን እንዳገኙና በዚህም ወገኖቻቸውን ለመርዳት ፅኑ ፍላጐት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ ከእኚህ የባህል መድሃኒት አዋቂ ከዶክተር ኢያሱ ኃ/ስላሴ ጋር በዕፅዋቶች ላይ ስለአደረጓቸው ምርምሮች፣ ስለባህል ህክምናቸውና የወደፊት ዕቅዳቸው ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

   እንዴት ነው ወደ ዕፅዋት ምርምር ዘርፍ የተሳቡትና ወደ ሙያው የገቡት?
ስለዕፅዋት የተፃፉ ጽሑፎችንና የምርምር ሥራዎችን የማንበብ ፍላጐትና ዝንባሌ ነበረኝ። ይህ ነገር ወደ ዕፅዋት ምርምር እንድሣብ፣ ስለ ‹0ፅዋቶች ዝርያ፣ አመጣጥና ጠቀሜታ ለማወቅ ፍላጐት እንዲያድርብኝ አድርጐኛል፡፡ ናይጀሪያ እየሰራሁ በነጀረበት ወቅት ፕሮፌሰር ላምቦ ከሚባል የታወቀ ሣይካትሪስት ሐኪም ጋር አብሮ የመሥራት ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ይህ ፕሮፌሰር ብዙውን ጊዜ በዕፅዋቶች ላይ ምርምር ሲያደርግና ሲጠቀም አየው ነበር፡፡
ይህ ሁኔታ እኔ ውስጥ ፍላጐት አሳደረብኝና ከእሱ ጋር እየዋልኩ ሁኔታውን ማጥናት ጀመርኩ። ናይጀሪያዎች በአንጐል መናወፅና ከሚጥል በሽታ ጋር በተያያዘ ብዙ ችግሮች ነበሩባቸው፡፡ በዚህ ፕሮፌሰር አማካኝነት ስለ እነዚህ በሽታዎች ብዙ ትምህርት አገኘሁ፡፡ እንግሊዝ አገር በነበርኩበት ጊዜም ለሪሰርች አንድ ትልቅ ላይብረሪ ስገባ የኢትዮጵያ ኸርባል ጥናቶች መጽሐፍ አገኘሁ፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ እንግሊዞች ወስደውት እዛው ያስቀሩትና በብራና የተፃፈው “መፅሐፈ መድሃኒት” የተባለውን በዚህ ላይብረሪ ውስጥ አግኝቼ ፎቶ ኮፒ በማድረግ ወሰድኩት፡፡ እነዚህን መጽሐፎች ሳነብ፣ በአገራችን በዕፅዋት ላይ የተደረጉ ምርምሮች እምብዛም አለመኖራቸውን ስመለከት ወደሙያው የበለጠ እንድሣብና እንዳጠና ተገፋፋሁ፡፡ ወደ አገሬ ከተመለስኩም በኋላ በዚሁ ዘርፍ ላይ የበለጠ መመራመርና የተፃፉ ነገሮችን ማንበብ ማዘውተሬ ወደ ሙያው እንድገባ የተገፋፋሁበት ምክንያቶች ናቸው፡፡
በአገራችን ያለው የባህል ህክምና ዕድገት ምን ይመስላል? በዘርፉ በቂ ጥናትና ምርምር ተደርጓል ብለው ያስባሉ?
በአገራችን በባህል መድሃኒቶች ምርምር ላይ የተሰማሩ ሰዎች እምብዛም የሉም፡፡ ሙያውን በዘመናዊ መንገድ ለማሳደግና ባለሙያዎችም ሙያቸውን ለትውልድ እንዲያስተላልፉ ለማድረግ የሚሰራ ሥራ የለም፡፡ “ኢትዮጵያን ኸርባል ሂስትሪ ውስጥ ተፅፎ እንዳገኘሁት፣ በአገራችን እስከዛሬ ከ80ሺ በላይ የሚሆኑ የባህል መድሃኒት አዋቂዎች አሉ፡፡ እነዚህ የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ሙያውን የሚተገብሩበት ሁኔታ ግን አሳዛኝ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ በአብዛኛው መድሃኒቱን የሚሰሩት ከሰው ተደብቀው ነው፡፡ ጓሮ ገብተው ተደብቀው ሰርተው ነው ለሰው የሚሰጡት፡፡ ይህ ደግሞ የመድሃኒቱን ንፅህና በማሳጣት ህመምተኛውን ለከፋ ችግርና አደጋ የሚያጋልጥ ይሆናል፡፡
ከዚህ ሌላ ደግሞ ባለሙያዎቹ ሙያውን ለሰዎች ለማሳየት አይፈልጉም፡፡ ምኑ ከምኑ ጋር ተዋህዶ መድሃኒት እንደሚሆን ማሳወቅ ፈጽሞ አይፈልጉም፡፡ ልጅ ካላቸው ለልጃቸው አሊያም በጣም ለሚወዱት ሰው ነው ሙያውን የሚያወርሱት፡፡ ያለበለዚያ ሲሞቱ ሙያው አብሮአቸው ይሞታል፡፡ ይህ ደግሞ ሙያው እንዳያድግና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ አድርጐታል፡፡ በየገዳማቱ፣ በየቤተክርስቲያናቱና በየመስጊዱ ውስጥ ተፅፈው የተቀመጡ የባህል ህክምናዎች አሉ፡፡ እነዚያን አውጥቶና አጥንቶ በግልጽ ህብረተሰቡ አንዲጠቀምበት የሚያደርግም ሆነ የሚያስተምር የለም፡፡
የኢትዮጵያ ምግብ ጥናት ድርጅት በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያስመሰግነው የሚችል ተግባር አከናውኗል። በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ጥናቶችን በማድረግ መጽሐፍም አሳትመዋል፡፡ ይህ ድርጅቱ ለህብረተሰቡ ያበረከተውን እጅግ ጠቃሚ የሆነ ነገር ነው፡፡ እዚያ መፅሐፍ ውስጥ የሌለ ነገር የለም፡፡ እኔ መጽሐፉን እንደማጣቀሻ ዋቢ (reference) ነው የምጠቀምበት። ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም አቅጣጫ ያሉ ብዙ ዓይነት ቅጠሎች ከፍተኛ የመፈወስ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ይህንን ማጥናትና ማወቅ፣ ህብረተሰቡ የሚጠቀምበትን መንገድ ማመቻቸት… ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡
የባህል ህክምና ከዘመናዊው ህክምና እኩል መሰጠት አለበት ብለው ያስባሉ? በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነትስ እንዴት ይገልፁታል?
የባህል መድሃኒት አሠራሩና ሁኔታው ከዘመናዊው ጋር ይመሳሰላል፡፡ ልዩነቱ የሚወስደው መድሃኒት መጠንና መድሃኒቱ የሚቀመምበት ሁኔታ ነው፡፡ የባህል መድሃኒቶች ክብራቸውን ይፈልጋሉ፡፡ ዕፅዋቶቹ የየራሳቸው ተፈጥሮአዊ ባህርይ ስላላቸው መድሃኒቶቹ የሚወዱትና የሚጠሉት ነገር አለ። መድሃኒቱን ስትወስድ፤ “ይህንን አታድርግ” ይህንን አድርግ ሊባል ይችላል፡፡ በዘመናዊም ይህ ነገር ያለ ነው፡፡ መድሃኒቶቹን ያረክሳል እየተባሉ የሚገልፁ ነገሮች አሉ፡፡ ዘመናዊ መድሃኒቶች በፋብሪካ ተዘጋጅተው የሚወጡ ስለሆነ ንፅህናቸው አስተማማኝ ነው፡፡ የባህል መድሃኒቶች ቅድም እንዳልኩሽ ተደብቀው የሚሰሩ በመሆናቸው የንፅህናቸው ጉዳይ አስተማማኝ የማይሆንበት ጊዜ ይኖራል፤ ሌላው የባህል መድሃኒቶች እንደ ዘመናዊዎቹ ሁሉ ከነርቭ ጋር ለተያያዙ ህመሞች በማሸትና በማሞቅ መፍትሔ ሊያስገኙ ይችላሉ። ለምሳሌ እኛ በማግኔቲክ ሲስተም፣ በሙቀትና ከዕፅዋት በተገኙ መድሃኒቶች በማሸት ብቻ ለወገብ ህመም መፍትሔ እያስገኘን ነው፡፡ ሴሎቹ እንዲከፈቱ እንዲፍታቱና ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችል ህክምና እየሰጠን ነው፡፡
ህክምናውን ለህመምተኞች ለመስጠት የሞከሩበት ሁኔታ የለም?
የመጀመሪያ ጥናትና ምርምር ያደረግሁት በወገብና በእግር ነርቮችና በአስም በሽታ ላይ ነበር፡፡ ይህንን አጥንቼ እንደጨረስኩ “ክርስቲና” በሚባለው የማህፀንና ፅንስ ህክምና ክሊኒኬ ውስጥ ህክምናውን መስጠት ጀመርኩ፡፡ ህክምናው የሚሰጠው በመቀባት ብቻ ነበር፡፡ የሚጠጣም ሆነ ሌላ ነገር አልነበረንም። የአስም ህሙማን መድኀኒቱን በአፍንጫቸው በመሳብ ብቻ ከህመማቸው የሚፈወሱበት መንገድ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የታካሚው ቁጥር እየጨመረ መጣ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በማህፀንና ፅንስ ክሊኒኩ ውስጥ መጨናነቅን ፈጠረ፡፡ ህክምናውን በተለየ ክሊኒክ ውስጥ መስጠት እንደምንችል የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ቢነግረንም በወቅቱ ይህንን ማድረግ ባለመቻላችን፣ ክሊኒኩ ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘጋ ተደረገ፡፡ ከዚያ በኋላ የማህፀንና ፅንስ ክሊኒኩ በድጋሚ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የባህል ህክምናውን ለጊዜው አቆምነው፡፡
እስከዛሬ ለምን ያህል ሰዎች ህክምናውን ሰጣችሁ? ለምን ያህል ህሙማን የፈውስ መፍትሄ አስገኝተናል ብላችሁ ታስባላችሁ?
 በወገብ፣ በሪህ፣ በአስምና ተጓዳኝ ህመሞች ተይዘው ይሰቃዩ ለነበሩ ከ800 በላይ ለሚሆኑ ህሙማን ህክምናውን ሰጥተን ፈውስ አስገኝተናል፡፡ በእኛ የባህል መድኀኒት ታክመው ለዓመታት የቆየና ነቀርሳ የሆነ በአንገት ላይ የነበረ ከፍተኛ ቁስለት ሙሉ በሙሉ እንዲድንና ታማሚው ከችግሩ እንዲፈወስ አድርገናል፡፡ ይህ በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ደስታን የሚሰጠኝና ሙያውን የበለጠ እንድወደው የሚያደርገኝ ጉዳይ ነው፡፡
አሁንስ ለምን ያህል በሽታዎች ፈውስ የሚሰጡ መድኀኒቶች አሏችሁ? መድኀኒቶቹ የሚወሰዱት በምን መልኩ ነው? የመድኀኒቶቹ አስተማማኝነትስ ምን ያህል ነው?
አስራ አንድ ለሚሆኑ የተለያዩ በሽታዎች መድኀኒቶች አሉን፡፡ መድኀኒቶቹ የሚወሰዱት ራስን ለችግር በማያጋልጥና በቀላል መንገድ ነው። እኛ የምንሰጠው መድኀኒት የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ በሰውነት ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ በአንገት .ላይ የሚደረጉ መድኀኒቶችም አሉን፡፡ ይህ እንግዲህ የሥነ ፍጥረት ምስጢር ነው፡፡ ዘመናዊ ሳይንስ ሊመልሰው የማይችል ነው፡፡ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ በመቀባት፣ በማሸት የሚሰጥ ህክምናም አለን፡፡ ከወይራ ዘይት ጋር እየተቀላቀሉ የሚሰሩ መድኀኒቶች አሉ፡፡ መድኀኒቶቻችን በሙሉ ግን የሚበሉ፣ የሚጠጡ አይደሉም፡፡ ወደሰውነት ውስጥ የሚገቡ መድኀኒቶች የሉንም፡፡
ይህንን ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ፍቃድስ አግኝታችኋል?
አዎን! በማህበራዊና የግል አገልግሎት ዘርፍ ህክምናውን ለመስጠት የሚያስችለን ፈቃድ አግኝተናል፡፡ ለህክምናው መስጫ የሚሆን ክፍልም አዘጋጅተን ለህሙማን መድኀኒት እየሰጠን እንገኛለን፡፡
ለአገልግሎታችሁ የምትጠይቁት ክፍያ እንዴት ነው?
እኛ ቀድሞውኑ አላማ አድርገን የተነሳነው ከህሙማን ገንዘብ መሰብሰብን አይደለም። በዘመናዊ ህክምና መፍትሄ ያላገኙ ህሙማን በባህላዊ መድኀኒት መፈወስ የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው፡፡ ለምንሰጠው ህክምና የምንጠይቀው ክፍያ እጅግ አነስተኛና ማንም ሰው በቀላሉ ሊከፍለው የሚችለውን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በርካታ ህሙማንን ያለምንም ክፍያ በነፃ ስናክም የቆየንበት ሁኔታ ሁሉ ነበር፡፡ የእኛ ዓላማ ህብረተሰቡ በባህላዊ መድኀኒት በቀላሉ ጤናውን ማግኘት እንደሚችል ማሳየት፣ ስለባህል መድኀኒት በሚገባ እንዲያውቅና መድኀኒቱን በራሱ መጠቀም እንደሚችል ማሳወቅ፣ ስለዕፅዋቱ ምንነት፣ ጠቀሜታቸውና አሰራሩ፣ የሚያስከትሏቸውን የጎንዮሽ ጉዳቶች ሁሉ በዝርዝር ለህብረተሰቡ ማሳወቅ ነው፡፡
በዕፅዋትና ባህላዊ መድሃኒቶች ላይ ያደረጓቸውን ጥናትና ምርምሮች አስመልክተው ያዘጋጁት ፅሁፍ አለ?
አዎ፡፡ በዘርፉ ያደረግሁትን ምርምርና ጥናት ሁሉ በፅሁፍ የማስቀመጥ ልምዱ አለኝ፡፡ እንደውም “ባህላዊ መድኀኒትና የጤና አጠባበቅ” በሚል ርዕስ ስር ያዘጋጀሁትና ለህትመት ዝግጁ የሆነ ሦስት ጥራዝ ፅሁፍ አለኝ፡፡ አሁንም እያጠራቀምኩ ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ወደ መፅሃፍነት ተቀይሮ ህብረተሰቡ እንዲያነበው፣ እንዲማርበትና በቀላሉ ጤናውን ለመጠበቅ የሚችልበትን መንገድ እንዲያውቅበት ለማድረግ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡
በአገራችን የባህል መድኀኒቶች በስፋት የሚገኙባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? በቀላሉ ከሚገኙና ለጤና ጠቃሚ ከሆኑ ባህላዊ መድኀኒቶች መካከል ጥቂቶቹን ቢገልፁልን?
በአገራችን በአብዛኛው የወይንአደጋ አካባቢ ባህላዊ መድኀኒቶች በስፋት የሚገኙባቸው አካባቢዎች ናቸው። በቆላና በደጋ አካባቢዎችም የሚገኙ መድኀኒቶች አሉ። በደብረዘይት ናዝሬትና አካባቢው መድኀኒቶቹ በስፋት ከሚገኙባቸው ቦታዎች የሚጠቀሱ ናቸው። እንደልብ ከሚገኙና በቀላሉ መፍትሄ ከሚሰጡን መድሀኒቶች መካከል ደግሞ እነ ዳማከሴ፣ ጤናአዳምና መሰል ነገሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ለምሳሌ ሰናፍጭ ሁላችንም በቀላሉ የምናገኘው ለእባጭ ፍቱን የሆነ መድኀኒት ነው፡፡ እነዚህን በቀላሉ አግኝቶ በመጠቀም ብዙ ገንዘብ ሊያስወጡ ከሚችሉ ቀላል የጤና ችግሮች መፍትሄ ማግኘት ይቻላል።
ዕፅዋቶቹን በኮስሞቲክስ ደረጃ ለመሥራትና ጥቅም ላይ ለማዋል ያደረጋችሁት ሙከራ አለ?
ዕፀዋትን በኮስሞቲክስ ደረጃ ለማዘጋጀት የሚያስችል ጥናት አድርገናል፡፡ ለተለያዩ የቆዳ ችግሮችና ለማድያት የሚውሉ መድኀኒቶችንም ሰርተናል፡፡ ይህን በዘመናዊ መንገድ በኮስሞቲክስ ደረጃ ለመስራትና ጥቅም ላይ ለማዋል ሃሳቡ ቢኖረኝም መሟላት የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ስላሉ አሁን ባለንበት ሁኔታ ይህንን ማድረግ አልቻልንም፡፡
በአንድ ወቅት ከጫት የወይን መጠጥ ሰርተው ከፍተኛ አድናቆትን አትርፈው ነበር? እሱ ጉዳይ የት ደረሰ?
ልክ ነው፡፡ እሱ ጉዳይ በአጋጣሚ የተደረገ ነበር፡፡ ለመድኀኒት የሚሆን ዕፅዋት ፍለጋ ወደ ደብረዘይት ስሄድ በአጋጣሚ አግኝቼ የገዛሁትን ጫት ወደ ወይን ለመለወጥ የሚያስችል ጥናት አድርጌና የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሜ እጅግ በጣም ጥሩ ጣዕም ያለው ወይን ለመስራት ችዬ ነበር፡፡ ጉዳዩ በወቅቱ ብዙ ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ ዶክተር በጫት ወይን ሰርቶ ህዝቡን ሊያሳብደው ነው ሁሉ ብለውኝ ነበር፡፡ የተሰራው መጠጥ ልዩ ጣዕም የነበረው ቆንጆ ነበር፡፡ ወይኑን የቀመሱ በርካታ ሰዎችም የሰጡኝ አስተያየት ይኸው ነበር፡፡ ግን ሥራው የሚሰራው በእጅ (ያለምንም ማሽን) በመሆኑ እጅግ አድካሚና ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነበር፡፡ እንደውም ወይኑ በተመረተ ሰሞን ከአሜሪካን አገር ስለዚሁ ጉዳይ ሊያነጋግሩኝ ሰዎች መጥተው ነበር፡፡ ስለአሰራሬ በደንብ ከጠየቁኝና ካጠኑ በኋላ ወደአገራቸው ሄደው ጫትን ወደ መርፌነት በመቀየር ከፍተኛ የአዕምሮ መናወፅ ላጋጠማቸው ህሙማን በመስጠት ህሙማኑ ከተያዙበት የጭንቀትና ድብርት ስሜት እንዲወጡ ለማድረግ ችለዋል፡፡ አሁን ከምን አደረስከው ላልሽኝ ሥራው ከፍተኛ ድካምና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ ለጊዜው እምብዛም አልገፋሁበትም፡፡
የማህፀንና ፅንስ ህክምና ሙያው በቃ ቀረ ማለት ነው?
ኧረ አልቀረም፡፡ ለምን ይቀራል፡፡ ለዓመታት የተማርኩበትና የሰለጠንኩበት ሙያማ አይቀርም፡፡ እሱንም እሰራለሁ፡፡ ግን ህብረተሰቡን ሴት ወንድ ሳይል ላገለግልበት የምችልበት ሙያ የባህል ህክምናው በመሆኑ በዚህ ሙያ የበለጠ ለመስራት እፈልጋለሁ፡፡  
የባህል መድኀኒት ዕውቀትና ጥበብ እንዲስፋፋ፣ ለመጪው ትውልድም እንዲተላለፍ መንግስት ምን ማድረግ አለበት ብለው ያስባሉ? በእርስዎስ በኩል ምን እያደረጉ ያሉት ጥረት አለ?
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 ሺ በላይ የባህል መድኀኒት አዋቂዎች ያሉ ቢሆንም በማህበር ተደራጅተው ያሉት ግን ከዘጠኝ ሺህ የሚበልጡ አይደሉም፡፡ ይህ ነገር በስፋት ሊሰራበት የሚገባና ህብረተሰቡን፣ መንግስትንም ሆነ አገርን ሊጠቅም የሚችል ትልቅ ተግባር በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት በአግባቡ ሊሰራ ይገባል ሌሎች አገራት ከባህል ህክምና እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ እያገኙ ነው፡፡ ለምሳሌ ጀርመን በዓመት ከ380 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ከባህል መድኀኒት ገቢ ታገኛለች፡፡ በአፍሪካ ውስጥ በስፋት የሚሰራባቸው አገራት ደቡብ አፍሪካና ሞሪሺየስ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ እኛ ዕፅዋቱ እያለን፣ ሃኪሙ እያለን አልተጠቀምንበትም፡፡ ስለዚህ ይህን ዕድል በስፋት ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታ ማመቻቸት፣ ሙያው ለትውልድ እንዲተላለፍ ማስተማር፣ በፅሁፍ ማቆየት ያስፈልጋል፡፡ በግሌ ህብረተሰቡን ለማስተማርና በርካታ ፅሁፎች፣ በመፃፍ ሙያውን ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ነኝ፡፡

Published in ዋናው ጤና
Page 4 of 16