ደራሲዋና አከፋፋዩ ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተዋል

“ፔላማ” የተሰኘው ፊልም በጥንቆላና በመፍትሄው ዙሪያ የሚያጠነጥን እንደሆነ የፊልሙ ደራሲና አዘጋጅ ሜሊ ተስፋዬ የገለፀች ሲሆን፣ ፊልሙ እምነታችንን የሚካ ነው በሚል ቅሬታ አንድ የእምነት ተቋም ለፖሊስ አቤቱታ አቀረበ፡፡ ሜሊ ተስፋዬና የፊልሙ አከፋፋይ ወደ ማዕከላዊ ምርመራ ተጠርተው ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ የፊልሙ በርካታ ተዋናዮችም ቃላቸውን ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ ፊልሙ ሃይማኖተን ይነካል የሚል ክስ ያቀረበው “ባፋ አባዩ ገዳ አንድነት የእምነት ተከታዮች ተቋም” መንፈሶቻችን ተነክተዋል፣ የሃይማኖት ተከታዮቻችን ተሰድበዋል ሲል ለፖሊስ አመልክቷል፡፡ ለእምነት የምንገለገልባቸውን ቁሳቁሶች ባካተተው ፊልም፤ ስማችን ጠፍቷል የሚለው ይሄው ተቋም፣ የእምነቱን ተከታዮች የሚያስጨንቅና የሚያሳቅቅ የድፍረት ስራ ተሰርቷል የሚል ክስ እንደቀረበባት ሜሊ ተስፋዬ ተናግራለች፡፡

“እኛ በፊልሙ ላይ የተጠቀሱትን መናፍስት የሚጠቀም የሃይማኖት ተቋም መኖሩን አናውቅም ነበር” የምትለው ሜሊ፤ ፊልሙ ከሁለት አመት በፊት በብሔራዊ ቲያትር ከተመረቀ በኋላ በተለያዩ የአገራችን ሲኒማ ቤቶች ከአገር ውጭም በዱባይ፣ በአቡዳቢ እና በሌሎች የአረብ ሀገራት እንዲሁም በጀርመን፣ በሆላንድ፣ በቤልጅየም፣ በፈረንሳይና በጣሊያን ከተሞች ፊልሙ ለእይታ መቅረቡንም ተናግራለች፡፡

በፖሊስ ፕሮግራም የተላለፉ የታምራት ገለታ ታሪኮች እንዲሁም “የአዳል ሞቴ” መንፈስ አለብኝ እያለ ብዙዎችን ያስጨነቀ የአንድ ጠንቋይ ታሪክ ለፊልሙ መነሻ እንደሆኑላት ትገልፃለች - ደራሲዋ፡፡ በዚህ መነሻ ጥናት አካሂዳ ፊልሙ እንደተሰራ ያወሳችው ሜሊ፤ ዋናው ገፀ ባህሪ በሀገራችን የሚታወቁትና አዳልሞቴ፣ ጠቋር፣ ወሰንጋላ የሚባሉ መናፍስትን እየጠራ ሰዎችን ሲያታልል፣ ገንዘባቸውን ሲበዘብዝና ለሞት ሲያበቃቸው ይታያል ብላለች፡፡ የፊልም ሙያዬን በመጠቀም ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስራ ለማቅረብ እንጂ የማንንም መብት ለመንካት አስቤ አልሰራሁም የምትለው ሜሊ፤ ለፖሊስ ቃሏን ከሰጠች በኋላ በዋስ እንደተለቀቀች ተናግራለች፡፡

Published in ዜና

በተጠርጣሪዎች ላይ የ240 ምስክሮች ቃል ተቀብያለሁ…ፀረ ሙስና ኮሚሽን
በ5 ኩባንያዎች ላይ የተጀመረው የኦዲት ስራ እስከ ሐምሌ 30 ይጠናቀቃል
አቶ ገ/ዋህድ ከመንግሥት የተሰጣቸውን መኖሪያ ቤት በ20 ቀን እንዲያስረክቡ ታዘዋል

 በሙስና ተጠርጥረው በታሰሩ የጉምሩክና ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊዎች ላይ ክስ ለመመስረት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለስድስተኛ ጊዜ የምርመራ ጊዜ እንዲራዘምለት ያቀረበው ጥያቄ ከተጠርጣሪዎች በኩል ተቃውሞ ቢገጥመውም የ10 ቀን ቀጠሮ ተፈቀደለት፡፡ የጉምሩክና ገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ዳሬክተር የነበሩት አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ከኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ የተሰጣቸውን መኖሪያ ቤት እንዲመልሱ ታዘዋል፡፡ ሰሞኑን ፍ/ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ከአቶ ገብረዋህድ ጋር በአንድ የምርመራ መዝገብ የተካተቱ 12 ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ፤ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአዳማ ቅርንጫፍ ኦፊሰር አቶ ያለው ቡለ እና የእንጀራ እናታቸው ወ/ሮ ሽቶ ነጋሽ በ13ኛ እና 14ኛ ተጠርጣሪ ሆነው እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

በተለያዩ የምርመራ መዝገቦች የተካተቱ ከ50 በላይ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ የ240 ምስክሮችን ቃል እንደተቀበለ የገለፀው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በርካታ ሰነዶችን እንዳሰባሰበና በአምስት ኩባንያዎች ላይ ኦዲት እያካሄደ እንደሆነ ገልጿል፡፡
በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ከማቅረቤ በፊት ከተጨማሪ ምስክሮች ቃል ለመቀበል፣ ቀሪ ሰነዶችን ለማሰባሰብና የኦዲት ስራዎችን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት ጠይቋል - ያስከስሳሉ የሚላቸውን ጭብጦችን በመጠቃቀስ፡፡ ቡድኑ ለጠቋሚ መክፈል የነበረበትን ገንዘብ አላግባብ ወስደዋል በሚል በአቶ ገ/ዋህድ እና በአቶ ጥሩነህን ላይ ባለፉት አስር ቀናት ተጨማሪ ሰነድ ሰብስቤያለሁ፣ የአምስት ምስክሮችን ቃል ተቀብያለሁ ያለው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል አላለም፡፡ ከቀረጥ ነፃ የገቡ መኪኖችን በሚመለከት ቀርቦ የነበረውን ክስ አላግባብ አቋርጠዋል በሚል በአቶ ገ/ዋህድ እና በሙሌ ጋሻው ላይ የአንድ ምስክር ቃል መቀበሉንና ከለገጣፎ የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡን ኮሚሽኑ ገልፆ፤ ከሦስት ተጨማሪ ምስክሮች ቃል ለመቀበል ጊዜ እንደሚያስፈልገው ጠቅሷል፡፡
ከውጭ የመጡ እቃዎች ሳይፈተሹ እንዲገቡ አድርገዋል ተብለው በተጠረጠሩት በአቶ ገ/ዋህድ፣ አቶ ነጋ፣ አቶ ሙሌ እና አቶ አሞኘ ላይ ተጨማሪ ሰነዶችንና ዲክለራስዮኖችን አሰባስቦ እንዳጠናቀቀና በአዳማ፣ በሚሌና ድሬዳዋ በተጀመረው ምርመራ የዘጠኝ ምስክሮችን ቃል እንደተቀበለ ኮሚሽኑ ለፍ/ቤቱ ገልጿል፡፡ ነገር ግን የአስር ተጨማሪ ምስክሮችና የአራት ባለሙያዎች ቃል ለመቀበል እንዲሁም መረጃዎችን ለማጠናቀር የጊዜ ቀጠሮ ያሰፈልገኛል ብሏል - ኮሚሽኑ፡፡
ወደ አዲስ አበባ በሚያጓጉዙት እቃ ላይ የታክስ ጉድለት የተገኘባቸው ኩባንያዎች ላይ በቃሊቲ ጣቢያ ድንገተኛ ፍተሻ እንዳይካሄድባቸው አድርገዋል ተብለው በተጠረጠሩት በአቶ ገ/ዋህድ፣ በአቶ ነጋ እና በአቶ አሞኘ ዙሪያም ምርመራውን ሲያካሂድ እንደሰነበተ የኮሚሽኑ ተወካዮች ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በዚሁ የፍተሻ ጉዳይ ከሰሞኑ የአራት ምስክሮች ቃል እንደተቀበለና ሰነዶች፣ እንደሰበሰበ ኮሚሽኑ ጠቅሶ፣ ቀሪ ምስክሮችና ሰነዶች እንዳሉ ገልጿል፡፡ ሁለት ተጠርጣሪዎች ተመሳጥረው የመንግስትን ታክስ አላግባብ ለራሳቸው ተጠቅመውበታል በሚል በአምስት በኩባንያዎች ላይ እንደተጀመረ የተናገሩት የኮሚሽኑ ተወካዮች፣ የሁለቱ ኩባንያዎች ኦዲት እንደተጠናቀቀና የሦስቱ ደግሞ እስከ ሃምሌ 30 ድረስ እንደሚጠናቀቅ ገልጿል፡፡
በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የተያዙ የኮንትሮባንድ እቃዎች አላግባብ እንዲለቀቁና ክስ እንዲቋረጥ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩት አቶ ገ/ዋህድ እና አቶ ጥሩነህ ላይ የሁለት ምስክሮች ቃል ተቀብሎ ሰነዶችንም እንዳሰባሰበ ኮሚሽኑ ጠቅሶ፤ የባለሙያዎችን ቃል ለመቀበልና ቀሪ ሰነዶችን ለማሰባሰብ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጿል፡፡
በፍራንኮቫሉታ እንዳይገባ የተከለከለ የውጭ አገር ሲሚንቶ አላግባብ እንዲገባ ተደርጓል በሚለው ጉዳይ ዙሪያ አምስት ሰነዶችን አሰባስቤያለሁ የሚለው ኮሚሽኑ፣ የእንግሊዝኛ ሰነዶችን ወደ አማርኛ ለማስተርጐምና ከሶስት ምስክሮች ቃል ለመቀበል ጊዜ ይሰጠኝ ብሏል፡፡ ይሄው የሲሚንቶ ጉዳይ አቶ ገ/ዋህድ፣ አቶ ነጋ እና አቶ አሞኘ እንዲሁም አቶ ተወልደን ይመለከታል፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን በማጠቃለያው በሁሉም ጉዳዮች ዙሪያ ምርመራዬን ለማጠናቀቅ የ14 ቀን ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሏል፡፡ ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው ካሁን በፊት እንዳደረጉት የኮሚሽኑን ጥያቄ በመቃወም መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ የሚጠይቀው፣ ተሰርቶ ባለቀ ጉዳይ ላይ ነው ያሉት የአቶ ገብረዋህድ ጠበቃ፤ ካለፉት ቀጠሮዎች ያልተለየ ተመሳሳይ ምክንያት እያቀረበ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብለዋል፡፡ ደንበኛቸው አቶ ገብረዋህድ ከባለቤታቸው ከኮ/ል ሃይማኖት ጋር መታሰራቸውን የገለፁት ጠበቃ፤ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እያለ፣ ህፃናት ልጆቻቸው የሚኖሩበትን መኖሪያ ቤት በ20 ቀናት ውስጥ እንዲያስረክቡ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ደብዳቤ ተልኮላቸዋል ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብቶ እግድ ትእዛዝ ይስጥልን በማለት የአቶ ገብረዋህድ ጠበቃ ቢጠይቁም፣ ፍርድ ቤቱ ግን ጉዳዩ በሌላ የአቤቱታ አቀራረብ እንዲቀርብ አዟል፡፡
አቶ ገብረዋህድ በበኩላቸው፤ “በአሁን ሰዓት ለነዚህ ልጆች እናትና አባታቸው መንግሥት ነው፤ ፍርድ ቤቱ የልጆቼን የመኖር መብት እንዲያረጋግጥልኝ በትህትና እጠይቃለሁ” ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ የምርመራ ጊዜ እንዲራዘምለት የሚያቀርባቸውን ነጥቦች በየጊዜው እያደሰና እየጨመረ ስለሆነ ለክርክር አመቺ አይደለም በማለት የተከራከሩ ሌሎች ጠበቆች በበኩላቸው፤ ሰነድ ለማስተርጐም እንዴት የጊዜ ቀጠሮ ይጠየቃል ሲሉ ኮሚሽኑን ተቃውመዋል፡፡ አዳዲስ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ወደ መዝገቡ በገቡ ቁጥር የጊዜ ቀጠሮው መቋጫ አይኖረውም በማለት መከራከሪያቸውን ያቀረቡት የተጠርጣሪ ጠበቆች፣ ስለዚህ ውሳኔ የሰጥበት ብለዋል፡፡ የዋስትና መብታችን ይከበር፣ ካልሆነም የጊዜ ቀጠሮዎች በጣም አጭር መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል ተጠርጣሪዎች፡፡
የወ/ሮ ሽቶ ነጋሽ ጠበቃ የደንበኛቸው ጉዳይ ተለይቶ እንዲታይ ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ሲሆን፤ በዝዋይ ገጠር ውስጥ የሚኖሩት ታታሪ ገበሬ ናቸው ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ሽቶ በሚቀጥለው አመት ለሚደረገው የአርሶ አደሮች ሽልማት በእጩ ተሸላሚነት ተመርጠዋል ያሉት እኚሁ ጠበቃ፣ አሁን ግን የግብርና ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻሉ ፍ/ቤቱ ተገንዝቦ በዋስ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ይፍቀድላቸው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው ችሎቱ፣ የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ፣ ከተጠየቀው የ14 ቀን ቀጠሮ ላይ 10 ቀን ብቻ በመፍቀድ ለሐምሌ 22 ቀጥሯል፡፡

Published in ዜና

ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎች አጀንዳ አድርገው ማራገባቸው ለሃገሪቱ መፃኢ እድል ጠቃሚ አለመሆኑንና ሁለቱም ወገኖች ከዚህ ድርጊት መታቀብ እንዳለባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አሳሰቡ፡፡ በደሴ ከተማ የእስልምና ሃይማኖት አባት በሆኑት በሼህ ኑሩ ይማም ላይ የተፈፀመውን ግድያ መንግሥት በቶሎ አጣርቶ ትክክለኛውን ውጤት እንዲያቀርብ ተጠይቋል፡፡ የመድረክ አመራር አባል የሆኑት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ የደሴ ከተማ የእስልምና ሃይማኖት አባት የነበሩት የሼህ ኑሩ ግድያን አጥብቀው እንደሚያወግዙና ገዳዮቻቸውም በፍጥነት ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

መንግሥት፤ ተቃዋሚዎች የሃይማኖት አጀንዳን እያራገቡ ነው የሚል ወቀሳ ማቅረቡን አልቀበለውም ያሉት ፕ/ር በየነ፤ የመብት ይከበር ጥያቄና የሃይማኖት ጥያቄ የተለያየ ነው ብለዋል፡፡ ጉዳዩን ያለቅጥ ማራገብና ማጦዝ በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን መግባባት ላይ ስለማያደርስ መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎች ጉዳዩን በጥንቃቄ ሊይዙት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ ሃይማኖት የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑ ተገቢ አለመሆኑን በማመልከት፣ ከተቃዋሚዎች ቀድሞ ወደዚህ ጉዳይ የገባው ኢህአዴግ ነው ብለዋል፡፡ “ኢህአዴግ ይህን ጨዋታ የጀመረው ምርጫ 97 ላይ ነው” የሚሉት ዶ/ር መረራ፤ መንግሥት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጁን በጉዳዩ አስገብቷል ይላሉ፡፡ “ሰሞኑን ደሴ ውስጥ በተገደሉት የሃይማኖት አባት የተነሳ ሃይማኖትን አጀንዳ አድርጐ እየተንቀሳቀሰ ያለው መንግሥት እንጂ ተቃዋሚዎች አይደሉም” የሚሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ እኛ ሃይማኖትን አጀንዳ የማድረግ እቅድም ሃሳብም የለንም ብለዋል፡፡

የኢዴፓ ሊ/መንበር ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ ደሴ ላይ የሃይማኖት አባት መገደላቸው በማንኛውም መንገድ ተገቢ አለመሆኑን አስምረው፣ መንግሥት ጉዳዩን ለህዝብ ግንኙነትና ለፕሮፓጋንዳ ከመጠቀም ይልቅ ገዳዮቻቸው ተገቢውን ፍርድ እንዲያኙ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ የመብት ጥያቄዎችም ህገ መንግሥቱን መሰረት ያደረጉ እስከሆኑ ድረስ በመንግሥት አካላት ሊወገዙ እንደማይገባ ጠቁመው እነዚህ ወገኖች መብታቸውን የሚጠይቁበትን ምቹ መድረክ መንግሥት ራሱ መፍጠር ይገባዋል ብለዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ በጉዳዩ ዙርያ የሰጡትን ሙሉ ቃል በገፅ 5 ላይ ይመልከቱ፡፡

Published in ዜና

የቦይንግ ኩባንያ ዘመናዊ ምርት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪም ላይነር አውሮፕላን (“B787”) ባለፈው አርብ ለንደን ደርሶ ካረፈ በኋላ ጭራው አካባቢ እሳት ተነስቶበት መለብለቡ የሚታወስ ሲሆን፤ የቃጠሎው መነሻ ከሬዲዮ መገናኛ አንቴና ጋር የተያያዘ እንደሆነ በምርመራ ተረጋገጠ፡፡ የእንግሊዝ የአየር አደጋ ምርመራ ክፍል ትናንት ባወጣው ሪፖርት፤ ከአውሮፕላኑ ጭራ አካባቢ የተተከለው አንቴና በመደበኛ በረራ ላይ አገልግሎት የማይሰጥ መጠባበቂያ አንቴና መሆኑን ገልጿል፡፡ የራሱ አነስተኛ ባትሪ ጋር የተገጠሙ አንቴና ላይ በሽቦዎች መጠላለፍ አልያም ባትሪው ላይ በተፈጠረ አንዳች እክል እሳት እንደተፈጠረ የምርመራ ክፍሉ ገልፆ፤ በተጨማሪ ምርመራ ትክክለኛው መንስኤ ከነመፍትሔው እስኪታወቅ ድረስ፣ መጠባበቂያውን አንቴና ለጊዜው በማላቀቅ አውሮፕላኖች ያለ ስጋት መብረር ይችላሉ ብሏል፡፡

አዲሱና ዘመናዊው ድሪም ላይነር (“B787”) ከወራት በፊት በዋናው የባትሪ ማስቀመጫ ቦታ እሳት በመነሳቱ፣ በመላው አለም ሁሉም “B787” አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ባትሪው ላይ የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጐ አውሮፕላኖቹ ወደ በረራ ከተመለሱ በኋላ እንደገና ተጨማሪ ችግር መፈጠሩ የቦይንግ ኩባንያን እና እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የ (“B787”) ቀዳሚ ተጠቃሚ ደንበኞች በእጅጉ አሳስቧቸው ነበር፡፡ ባለፈው አርብ የተፈጠረው ችግር ለክፉ የሚሰጥ እንዳልሆነ በምርመራ ተረጋግጦ ትናንት በይፋ ከተነገረ ወዲህ፣ የቦይንግ የአክሲዮን ዋጋ ወዲያውኑ እንዳንሰራራ ተገልጿል፡፡

Published in ዜና

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በያዝነው ዓመት ከተለያዩ የታክስና የቀረጥ ምንጮች ከ84 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ለአዲስ አድማስ በላከው መረጃ አስታወቀ፡፡ ዘንድሮ የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ13.5 ቢሊዮን ብር እንደሚበልጥ ተገልጿል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ የላከው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዘንድሮ ዓመት ከ2003 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ በሦስት አመታት ውስጥ 201 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ነበር፡፡

ከተለያዩ ታክሶችና የገቢ ምንጮች የተሰበሰበው ገንዘብ ግን ከእቅዱ በላይ 206 ቢ. ብር ገደማ እንደሆነ ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡ በየአመቱ በሚሰበሰበው ታክስ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ የሚታየው ግን በአዲስ አበባ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ብቻ ታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤት ገቢዎች ዘንድሮ 9.15 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ፣ 9.34 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጿል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ4.18 ቢሊዮን ብር (የ81%) ጭማሪ ማሳየቱን መረጃው ያመለክታል፡፡

Published in ዜና

በአዲስ አበባ የፈረሱና ለመልሶ ማልማት ሥራ የተዘጋጁ የተለያዩ ቦታዎች የወንጀለኞች መሸሸጊያ እየሆኑ መምጣታቸውንና ህገወጦች ለዝርፊያና ወንጀሎችን ፈፅሞ ለመሸሸጊያ እያዋሏቸው እንደሆነ ተጠቆመ፡፡ አስተዳደሩ ችግሩን ለማስወገድ ጥረት አደርጋለሁ ብሏል፡፡ በከተማው ለኮንደሚኒየም ቤቶች ግንባታና ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በሚል ምክንያት እየፈረሱ ባሉት ቦታዎች በህገወጥ የዘረፋና የስርቆት ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎች እየተገናኙ የሚሸሸጉበት፣ ዘርፈው ከፖሊስም ሆነ ከህብረተሰቡ እይታ የሚሰወሩበት እንዲሁም የተለያዩ ጥቃቶችን ለማድረስ የሚገለገሉበት ስፍራ እየሆነ መምጣቱን የጠቆሙት ነዋሪዎች፤ ችግሩን መንግሥት በቸልተኝነት ሊመለከተው እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ኃ/ማርያም ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይህንኑ ጉዳይ አንስተው ሲናገሩ፤ ከተማዋ በፈጣን እድገት ላይ በመሆኗ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ህገወጥ ተግባራት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህን ህገወጥ ተግባራት ለማስወገድና ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ የሚገባበትን ሁኔታ ለመፍጠር ተግተን እንሰራለን ብለዋል፡፡ የተማዋን የፀጥታ ጉዳዮች አስመልክተው ሲናገሩም፤ አስተዳደሩ የከተማዋን ፀጥታ አስተማማኝና ቀጣይ ለማድረግ ካለበት ከፍተኛ ኃላፊት በመነሳት፣ የነዋሪውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በከተማዋ በኃይማኖት ሽፋን የሚፈፀሙ ህገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከከተማ እስከ ወረዳ ላሉ ለስድስቱም ሃይማኖቶች የጋራ ምክር ቤት አባላት ስልጠናዎች መስጠታቸውንም ገልፀዋል፡፡ በከተማዋ ውስጥ በርካታ የጥበቃ ማዕከሎች ግንባታ የተከናወነ ሲሆን ጥበቃዎችን በመቅጠር የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

በአክሲዮን ሽያጭ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ በአምስት አመታት ከ80 ሚ.ብር በላይ ለማግኘት ያልቻለው የህብር ስኳር አክሲዮን ማህበር፤ የባለአክሲዮኖች እልባት ያጣ ውዝግብ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፤ በርካታ ባለአክሲዮኖች ለንግድ ሚኒስቴር በድጋሚ አቤቱታ አቀረቡ፡፡ ከጠቅላላው የአክሲዮን ሽያጭ 8 በመቶ ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖች በድጋሚ ባቀረቡት አቤቱታ፤ የንግድ ሚኒስቴር ጣልቃ እንዲገባ የጠየቁ ሲሆን፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጣልቃ ገብቶ ምርመራ ማካሄድ የሚችለው ቢያንስ አስር በመቶ ድርሻ የያዙ አባላት አቤቱታ ሲያቀርቡ ነው ተብሏል፡፡

አክሲዮን የገዛነው የምስረታ ሂደቱን የሚመሩ የቦርድ ሃላፊዎች በውሸት ማስታወቂያ ስላታለሉን ነው በማለት በፍርድ ቤት ክስ የመሰረቱ አባላት፤ የተሰበሰበው ገንዘብ በዝግ አካውንት መቀመጥ ሲገባው ለብድር አገልግሎት ውሏል ይላሉ፡፡ “መስራቶቹ ለስኳር ምርት መሬት ተሰጥቶናል ብለው ዋሽተውናል” የሚሉት አባላት፤ በፍ/ቤት እየተከራከሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የአክሲዮኑ መስራቾች በበኩላቸው፤ የተሰበሰበው ገንዘብ ያለአገልግሎት ከሚቀመጥ ለጊዜው ደህና ወለድ ቢገኝበት ይጠቅማል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

መጀመሪያ ላይ ቃል የተገባልንን መሬት ልናገኝ ባንችልም ምትክ መሬት ተሰጥቶን ነበር ብለዋል፡፡ አቤቱታ አቅራቢ ባለአክሲዮኖች ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ከመነሻው የአክሲዮኑ ምስረታ በቂ ጥናት ያልተደረገበት ሰነድ በማቅረብ የተጀመረ ስለሆነ ለጉዳት ዳርጐናል የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ በሦስት አመት ውስጥ ከአክሲዮን ሽያጭ 600 ሚሊዮን ብር፣ ከመንግስት ብድር ደግሞ 1.4 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ የፋብሪካ ተከላና የስኳር አገዳ ልማት ይጀመራል የሚለው እቅድ ፈቅ አላለም ብለዋል፡፡

የስምንት በመቶ ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖች አቤቱታቸውን በደብዳቤ ሲያቀርቡ ከንግድ ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ ጋር እንደተነጋገሩ ገልፀዋል፡፡ የንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ምክትል ሃላፊ አቶ አብዱራህማን ሰኢድ፣ ባለአክሲዮኖቹ የአቤቱታ ደብዳቤ እንዳስገቡ ገልፀው፤ በንግድ ህግ መሠረት ንግድ ሚኒስቴር ጣልቃ የሚገባው ቢያንስ አስር በመቶ የሚሆኑ ባለአክሲዮኖች ቅሬታ ሲያቀርቡ ነው ብለዋል፡፡ የማህበሩ አካሄድ ላይ የማታለል ድርጊቶች የሚፈፀሙ ከሆነ ወይም የተወሰኑ ባለአክሲዮኖችን ለይቶ የሚጐዳ ነገር የሚሰራ ከሆነ ሚኒስቴሩ ጣልቃ እንደሚገባ አቶ አብዱራማን ጠቅሰው፣ በህብር ስኳር ጉዳይ የቀረበውን አቤቱታ ከህጉ ጋር ተገናዝቦ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የህብር ስኳር ምስረታ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

Published in ዜና

ታላቁ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ወደ ፖለቲካ ለመግባት ፍላጎት እንዳለውና የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ለመሆን እንደሚያስብ በመናገሩ ትኩረት ሳበ፡፡ በሳምንቱ መግቢያ ላይ አሶስዬትድ ፕሬስ አትሌቱን በማነጋገር ያሰራጨውን ዘገባ በመንተራስ በርካታ የዜና አውታሮች እና መረቦች ጉዳዩን በተለያየ አቅጣጫ በመተንተን ዘግበውታል፡፡ ፎክስ ኒውስ አዲስ አይነት ፉክክር ውስጥ መግባቱን በርእሱ ሲገልፅ፤ የኬንያው ዴይሊ ኔሽን ኃይሌ ፖለቲካ ሊገባ ነው በሚል ዜናውን አናፍሷል፡፡

ዘ አፍሪካን ሪፖርት በበኩሉ አትሌቱን ከጆርጅ ዊሃ በማነፃፀር ባሰራጨው መጣጥፍ ኃይሌ ከስፖርት ወደ ፖለቲካ ዓለም በመዞር የአገር ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚያበቃ የተሻለ ስትራቴጂ እንዳለው ደምድሟል፡፡ ምንም እንኳን ቤተሰቡ ያሰበውን ስለማሳካቱ እርግጠኛ ባይሆኑም ኃይሌ ፖለቲካን የፈለገው የብዙ ወገኑን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሆነ ለአሶስዬትድ ፕሬስ የገለፀ ሲሆን ህዝብን የበለጠ የሚረዳበት እድል ማጣት እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የፓርላማ ተመራጭ ሆኖ ለመወዳደር እቅድ እንዳለው በትዊተር ማስታወሻው እንደፃፈም በርካታ የዓለም ሚዲያዎች ገልፀዋል፡፡ ምርጫ እንደሚወዳደር እና ኢትዮጵያ በእድገት ወደፊት እንድትራመድ ልረዳት አፍለጋለሁ ማለቱ ተዘግቧል፡፡

ዘ አፍሪካን ሪፖርተ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ጆርጅ ዊሃን ያነፃፀረበትን መጣጥፍ ያቀረበው የስፖርት ስኬት የአንድ አገርና ህዝብን የወደፊት እጣ ፋንታ ለማስተዳደር ይበቃል ወይ በሚል ጠያቂ ርእስ ነበር፡፡ በአፍሪካ አህጉር በስፖርት ስኬት እና ዝናው ወደ ፖለቲካ በቀጥታ በመግባት ብቸኛው የላይቤሪያው ጆርጅ ዊሃ እንደነበር ያወሳው ዘ አፍሪካን ሪፖርት ከስፖርት ወደ ፖለቲካ ዓለም መግባት በአውሮፓ እና በአሜሪካ የተለመደ መሆኑን በማመልከት ነው፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ጆርጅ ዊሃ ከስፖርቱ ዓለም በቀጥታ ወደ ላይቤርያ ፖለቲካ በመግባት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የወሰነው በተሟላ ስትራቴጂ አልነበረም የሚለው ዘ አፍሪካን ሪፖርት በወቅቱ ተፎካካሪው የነበሩትን ሄለን ጆሴፍ ሰርሌፍ ማሸነፍ ሳይሆንለት መቅረቱን አስታውሷል፡፡

እንደ ዘ አፍሪካን ሪፖርት ማብራርያ ኃይሌ ከስፖርቱ ወደ ፖለቲካው ዓለም በቀጥታ አልገባም፡፡ በስፖርቱ ባገኘው ስኬት እና ዝና፤ በማህበራሰባዊ ግልጋሎቶች፤ በኢንቨስትመንት መስክ ባገኛቸው ውጤቶች በኢትዮጵያውያን ክብርና አድናቆት አግኝቷል በብሄራዊ ጉዳዮች ባለው የአገር አዋቂነት ሚና እና የአገር ሽማግሌነት አስተዋፅኦ የተመሰገነበት ተግባራቱ ናቸው፡፡ በርካታ የተቃዋሚ መሪዎችና ፖለቲከኞች በመንግስት ጥፋተኛ ሆነው ከታሰሩበት ቅጣት በይቅርታ ምህረት ተደርጎላቸው እንዲፈቱ ካአገር ሽማግሌዎች ዋናው ተፅእኖ ፈጣሪ እንደነበር በዘ አፍሪካን ሪፖርት ሃተታ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ኃይሌ አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት በሚያስችል ፉክክር ለመግባት የፈለገው ከ2 ዓመታት በኋላ በግል ተወዳዳሪነት ፓርላማ ተመርጦ ከተሳካለት መሆኑን በመግለፅም ዘ አፍሪካን ሪፖርት ኃይሌ በፕሬዝዳንትነት አገሩን ለመምራት ያለው ስትራቴጂ ከጆርጅ ዊሃ የተሻለ ያደርገዋል በሚል ደምድሟል፡፡
በሌላ በኩል ኃይሌ ገብረስላሴ በኦሎምፒኳ ከተማ ሉዛን ውስጥ በ‹ዘ አሶሴሽን ኢንተርናሲዮናሌ ዴላ ፕሬስ ስፖርትስ› ልዩ ክብር ሽልማት ተሰጥቶታል፡፡ ሽልማቱ AIPS Power of Sport Award ተብሎ ይጠራል፡፡ በየዓመቱ በስፖርቱ ዓለምን፤ አገርንና ማህበረሰብን የሚለውጥ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የስፖርት ሰዎች የሚሰጥ ልዩ የክብር ነው፡፡ 86 ዓመታት እድሜ ያለው ዓለም አቀፉ ተቋም “ኤአይፒኤስ” የሽልማት ስነስርዓቱን ዘንድሮ ያዘጋጀው ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ጃኩዌስ ሬጌ እና አሜሪካዊቷ የቀድሞ ዋናተኛ ዶና ዴሳሮና ሌሎቹ ተሸላሚዎች ናቸው፡፡ ሽልማቱ በአትሌት ምስል የተዘጋጀ ቅርፅ ሲሆን በቻይናው የኦሎምፒክ ምርቶች አምራች እና አከፋፋይ ኩባንያ ሆናቭ የተዘጋጀ ነው፡፡

ኃይሌ ገ/ስላሴ ለዚህ ክብር ለመመረጥ የበቃው በአትሌቲክስ ስፖርት ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ውጤት በመቆየቱ፤ በስፖርቱ ያለው ተወዳጅነት በአገሩ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በመሆኑ፤ በጂ4ኤስ ታዳጊዎች ፕሮግራም 14 ወጣት አትሌቶች በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎ እንዲያገኙ በፈጠረው መነቃቃት እና በሰጠው ድጋፍ፤ በፀረ ኤድስ ዘመቻ ለአመታት ባበረከተው አስተዋጽኦ፤ በአፍሪካ ትልቁ የሆነውና እስከ 37ሺ ስፖርተኞችን በማሳተፍ የሚታወቀውን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በመመስረትና በዚሁ ስር የሚካሄዱ ውድድሮችን በተለያዩ የተባበሩት መንግስታት እና የበጎ አድራጎት ተቋማት ብሄራዊ መልዕክቶች አያይዞ የፈፀማቸው ተግባራት እውቅና በማግኘታቸው ነው፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ ተመሳሳይ ሽልማት ሲያገኝ የመጀመርያው አይደለም፡፡

ከ2 ዓመት በፊት በስፔን ትልቅ ክብር የሚሰጠውን‹ፕሪንስ ኦስተሪዬስ አዋርድስ ፎር ስፖርትስ› ተቀብሏል፡፡ ሽልማቱ በስፖርት የሰው ልጅን የላቀ ብቃት እና ችሎታ ያሳደገ አትሌት በመባል ከስፔን ንጉሳውያን ቤተሰብ እጅ የተረከበው ነው፡፡ ኃይሌ በወቅቱ ይህን ሽልማት የወሰደው ከታዋቂው ኳስ ተጨዋች ራውል ጎንዛሌዝ ጋር በመፎካከር ነበር፡፡ ‹ፕሪንስ ኦስተሪዬስ አዋርድስ ፎር ስፖርትስ› የተባለው የክብር ሽልማት በጆኖ ሚር የተባለ ቀራፂ የተሰራ ቅርፅ፤50ሺዩሮ፤ ዲፕሎማና የሽልማቱ አዘጋጅ ፋውንዴሽን አርማ የተቀረፀበት ስጦታን የሚያካትት ነው፡፡

 

                        ከወር በኋላ በራሽያዋ መዲና ሞስኮ ለሚካሄደው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ምርጫ እና ዝግጅት በተመለከተ በግልፅ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ኬንያ ተሳታፊ ቡድኗ ለመምረጥ ባዘጋጀችው ብሄራዊ ሻምፒዮና ላይ ሰሞኑን ከፍተኛ ትኩረት አድርጋ ቆይታለች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በዓለም ሻምፒዮናው በስንት የውድድር መደቦች እንደሚሳተፍ እና ስንት አትሌቶችን እንደሚልክ አለማሳወቁየሚኖረውን ዝግጅት እንዳያስተጓጉል ተሰግቷል፡፡ ከወር በፊት በአሜሪካ ዩጂን በተደረገው የፕሮፈንታይኔ ክላሲክስ ውድድር በ10ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ለዓለም ሻምፒዮናው የሚመረጡ አትሌቶችን ለመለየት ፌደሬሽኑ ተጠቅሞበታል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ከሚጠይቀው ሚኒማ ባሻገር በየውድድር መደቡ ለሁሉቱም ፆታዎች ለእያንዳንዳቸው ሶስት ምርጥ አትሌቶችን ለመመልመል ስለሚከተለው አሰራር ግልፅ መረጃ አለመኖሩ ግን የሚያሳስብ ይሆናል፡፡

በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ውጤታማ የሆኑ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው የዝግጅት ወቅት ካለባቸው የውድድር መደራረብ አንፃር ብቃታቸው የወደ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ በትልልቅ የዓለም ማራቶን ውድድሮች ያሸነፉ በርካታ ማራቶኒስቶች መኖራቸውም ለምርጫ ማስቸገሩ አይቀርም፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው በምታሳትፈው ቡድን ምርጫ ላይ ውስብስብ ችግሮች እንደሚኖሩም ይገመታል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ኬንያ የዓለም ሻምፒዮና ተሳታፊ ቡድኗን የምትመርጥበት አይነት ተመሳሳይ ብሄራዊ ሻምፒዮናን በአሰላ ከተማ በሚገኘው አረንጓዴ ስታድዬም ማካሄዱ አይዘነጋም፡፡ ከ35 በላይ የክልል፤የከተማ መስተዳድሮችን፤ የክለብ እና የብሄራዊ ቡድን ውክልና ያላቸው 1070 አትሌቶችን ያሳተፈው ብሄራዊ ውድድር በጋራድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አብይ ስፖንሰርነት 42ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚል ስያሜ የተዘጋጀ ነበር፡፡ የመከላከያ አትሌቲክስ ቡድን አጠቃላይ አሸናፊ በሆነበት ብሄራዊ ሻምፒዮናው በ5 የስፖርት አይነቶች ብሄራዊ ሪከርዶች ከመሻሻላቸውም በላይከ1 በላይ የወርቅ ሜዳልያ የተጎናፀፉ 5 አትሌቶችም ተገኝተውበታል፡፡

ይሁንና ይህ ብሄራዊ ሻምፒዮና በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ስለሚወክለው ቡድን ምንም የሰጠው ፍንጭ አልነበረም፡፡ በተያያዘ ግን የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመመልመል ዓመታዊ ብሄራዊ ሻምፒዮናውን ዛሬ በናይሮቢ ከተማ በሚገኘው ናያዮ ስታድዬም ያካሂዳል፡፡ ብሄራዊ ሻምፒዮናው ምርጥ እና ልምድ ያላቸው ፤ወጣት እና አዳዲስ አትሌቶችን በዓለም ሻምፒዮናው ቡድን ለማካተት የተዘጋጀ እንደሆነ ሲታወቅ በኬንያ ከፍተኛ ተመልካች የሚያገኝ የአትሌቲክስ ውድድር እንደሆነና ሳፍሪኮም በተባለ የቴሌኮም ኩባንያ በ23ሺ ዶላር የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ እንደተዘጋጀ ተገልጿል፡፡ በዚሁ ሻምፒዮና በ10 የአትሌቲክስ ስፖርቶች መሳተፍ እንዲችሉ አስፈላጊውን ሚኒማ ያሟሉ፤ ከሁለት ዓመት በፊት የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆኑ 192 አትሌቶች (132 ወንድ እና 60 ሴት) ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን በየውድድር አይነቱ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ማግኘት የሚችሉት በቀጥታ ለዓለም ሻምፒዮናው ቡድን የመመረጥ እድል እንዳላቸው ታውቋል፡፡ በብሄራዊ ሻምፒዮናው 3ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች አስቀድሞ በነበራቸው ውጤት ግምገማ ተደርጎ የመመረጥ እድል ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ በብሄራዊ ሻምፒዮናው የተመረጡ አትሌቶች ከአንድ ሳምንት በኋላ በካሳራኒ በሚገኘው የመኖርያ እና የልምምድ ካምፕ በመግባት የመጨረሻ ዝግጅታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ኬንያ ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በመካከለኛ ርቀት፤ በ5ሺ ሜትርና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች እና በማራቶን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ የሚበቃ የቡድን ስብስብ እንደሚኖራት ትጠብቃለች፡፡ አይኤኤኤፍ ሰሞኑን እንዳስታወቀው ከ200 አገራት የተወከሉ 2000 አትሌቶች የሚሳተፉበት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በመላው ዓለም በሚኖረው የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት በሪከርድነት የሚመዘገብ ተመልካች ያገኛል፡፡ በርካታ የዓለም ክፍሎችን በቴሌቭዥን ስርጭት ለማዳረስ ስምምነቶች መደረጋቸውን የገለፀው ዓለም አቀፉ የአትሌቲክሰ ፌደሬሽኖች ማህበር ለ9 ቀናት የሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮናው በ200 አገራት ሽፋን እንደሚኖረውና የሚያገኘው ድምር ተመልካች እስከ 5 ቢሊዮን እንደሚገመት አስታውቋል፡፡ ከ2 አመት በፊት በደቡብ ኮርያ ዳጉ ተደርጎ በነበረው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኬንያ 47 አትሌቶችን በማሳተፍ በ17 ሜዳልያዎች (7 የወርቅ፤ 6 የብርና 4 የነሐስ) ከዓለም ሶስተኛ ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃ አግኝታ እንደነበር ሲታወስ፤ ኢትዮጵያ በ34 አትሌቶች ተካፍላ 5 ሜዳልያዎችን (1 የወርቅና 4 የነሐስ) በማግኘት ከዓለም ዘጠነኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ነበረች፡፡ ባላፉት 13 የዓለም ሻምፒዮናዎች ደግሞ ኬንያ በተሳትፎ ታሪኳ በሰበሰበቻቸው 100 ሜዳልያዎች (38 የወርቅ፤ 33 የብርና 29 የነሐስ) ከዓለም በሶስተኛ ደረጃ ላይ ስትመዘገብ፤ ኢትዮጵያ በ54 ሜዳልያዎች(19 የወርቅ፤ 16 የብርና 19 የነሐስ) 7ኛ ላይ ናት፡፡

በደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ አርታኢነት ሰላሳ ፀሐፍት ገጣሚያንና ሰዓሊያን በስብሐት ገብረእግዚብሔር ህይወትና ሥራ ላይ ያቀረቧቸው ፅሁፎች የተካተቱበት “መልክዐ ስብሀት” የተሰኘ መጽሐፍ የፊታችን ሰኞ በ11 ሰዓት በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መፅሐፉ በደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ሥራና ህይወት ላይ የሚያተኩር እንደሆነ ታውቋል፡፡
ፅሁፎቻቸው በመፅሐፉ ከተካተቱ ፀሐፍት መካከል ሃያሲ አስፋው ዳምጤ፣ ቴዎድሮስ ገብሬ፣ ሌሊሳ ግርማ፣ አዳም ረታ፣ ኢዮብ ካሣ፣ ሚካኤል ሽፈራው፣ ነቢይ መኮንን፣ አልአዛር ኬ፣ አውግቸው ተረፈ የሚገኙበት ሲሆን ከሰዓሊያን ደግሞ በቀለ መኮንን፣ ፍፁም ውብሸት፣ ቴዲማን ተካትተዋል፡፡
መፅሐፉ ሲመረቅ ነቢይ መኮንን፣ ታገል ሰይፉ፣ በቀለ መኮንን፣ ተፈሪ አለሙ እና ሌሎችም ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡
“መልክዐ” በሚል ቅድመ ግንድ ተከታታይ መፅሐፍት ለመታተም መታቀዱንና “መልክዐ ፀጋዬ ገብረመድህን” በዝግጅት ላይ መሆኑን የገለፀው አርታኢው፤ ስለ ስብሃት የታተመው “መልክዐ ስብሐት” መድበል ሚዛናዊነቱን የጠበቀ እንዲሆን ጥረት መደረጉን ተናግሯል፡፡

Page 7 of 13