የጸረ ሽብርተኝነት ህጉ ይሻሻል ብለዋል
ከዚህ በፊት በሽብርተኝነት የተፈረደባቸው እንዲፈቱ ጠይቀዋል
41 የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የፕሬስ ነጻነት አቀንቃኞች፣ አለማቀፍና ክልላዊ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትና የሙያ ማህበራት መንግስት በቅርቡ የሽብርተኝነት ክስ የመሰረተባቸውን ጋዜጠኞችና የዞን 9 ጦማርያን በአፋጣኝ እንዲፈታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከትናንት በስቲያ በላኩት ደብዳቤ መጠየቃቸውን ብሉምበርግ ኒውስ ዘገበ፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ አርቲክል 19 ምስራቅ አፍሪካ፣ ሲቪል ራይትስ ዲፌንደርስ፣ ወርልድ አሊያንስ ፎር ሲቲዝን ፓርቲሲፔሽን፣ ፔን አሜሪካና የመሳሰሉት አለማቀፍ ድርጅቶች በጋራ በጻፉት ደብዳቤ፣ መንግስት ጋዜጠኞችንና ጦማርያንን በሽብርተኝነት እየከሰሰ ለእስር መዳረጉን መቀጠሉ ያሳስበናል፣ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ መገታት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ሶስቱ ጋዜጠኞችና ስድስቱ ጦማርያን ሶስት ወራት ለሚሆን ጊዜ ይህ ነው የሚባል ክስ ሳይመሰረትባቸው ያለአግባብ በእስር ላይ መቆየታቸውንና አንዳንዶቹም በምርመራ ወቅት እንግልት እንደደረሰባቸው መናገራቸውን የጠቀሰው ደብዳቤው፣ ይህም አግባብ አለመሆኑን ገልጿል፡፡
ጋዜጠኞቹና ጦማርያኑ በተመሰረተባቸው የሽብርተኝነት ክስ በረጅም አመታት እስር ብሎም በሞት ሊቀጡ እንደሚችሉ ስጋታቸውን የገለጹት ድርጅቶቹ፤ ይህም አለማቀፍ ህጎችን የሚጥስና በቀጠናው የተረጋጋ ሰላምና ደህንነት ለመፍጠር የሚደረገውን አለማቀፍ ጥረት ዋጋ የሚያሳጣ እርምጃ ይሆናል ብለዋል፡፡
መንግስት አግባብነት በሌለው የጸረ ሽብርተኝነት ህግ በቁጥጥር ውስጥ አውሎ ክስ የመሰረተባቸውን ጋዜጠኞችና ጦማርያን በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቅ አስፈላጊውን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ጥያቄ ያቀረቡት እነዚህ ድርጅቶች፤ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በጸረ ሽብር ህጉ ተከሰው የተፈረደባቸው ዜጎች ጉዳይ አግባብ አለመሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሳይቀር እንዳመነበትና እንዳወገዘው አስታውሰዋል፡፡
ከጋዜጠኞቹና ከጦማርያኑ በተጨማሪም፣ ከዚህ በፊት በሽብርተኝነት ተከሰውና ተፈርዶባቸው ያለአግባብ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ መንግስት በአፋጣኝ እንዲፈታና የጸረ ሽብርተኝነት ህጉንም አለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መስፈርቶችን በሚያሟላ መልኩ እንደገና አሻሽሎ እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል፡፡ኢትዮጵያ የአለማቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነትና የአፍሪካን የሰብዓዊና የህዝብ መብቶች ኮንቬንሽን ፈርማ የተቀበለች ሃገር እንደመሆኗ፣  መንግስት አለማቀፍ ህጎች የጣሉበትን ግዴታ በማክበር መሰረታዊ መብቶቻቸው ተጥሰው ለእስር የተዳረጉ ዜጎችን በሙሉ ከእስር እንዲለቅ ጠይቀዋል፡፡
ደብዳቤውን የጻፉት ድርጅቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. Amnesty International 
2. ARTICLE 19 Eastern Africa 
3. Central Africa Human Rights Defenders Network (REDHAC), Central Africa 
4. CIVICUS: World Alliance for Citizen Participation 
5. Civil Rights Defenders, Sweden 
6. Coalition pour le Développement et la Réhabilitation Sociale (CODR UBUNTU), Burundi 
7. Committee to Protect Journalists 
8. Community Empowerment for Progress Organization (CEPO), South Sudan 
9. Conscience International (CI), The Gambia 
10. East and Horn of Africa Human Rights Defenders Project 
11. Egyptian Democratic Association, Egypt 
12. Electronic Frontier Foundation 
13. Ethiopian Human Rights Project (EHRP) 
14. Elma7rosa Network, Egypt  15. English PEN 
16. Freedom Now 
17. Front Line Defenders, Dublin  18. Human Rights Watch 
19. International Women’s Media Foundation (IWMF) 
20. Ligue des Droits de la personne dans la region des Grands Lacs (LDGL), Great Lakes 
21. Ligue Iteka, Burundi 
22. Maranatha Hope, Nigeria 
23. Media Legal Defence Initiative
24. National Civic Forum, Sudan 
25. National Coalition of Human Rights Defenders, Kenya 
26. Niger Delta Women’s movement for Peace and Development, Nigeria 
27. Nigeria Network of NGOs, Nigeria  
28. Paradigm Initiative Nigeria, Nigeria  
29. PEN American Center  30. PEN International  
31. Réseau africain des journalistes sur la sécurité humaine et la paix (Rajosep), Togo  
32. Sexual Minorities Uganda (SMUG), Uganda  
33. South Sudan Human Rights Defenders Network (SSHRDN), South Sudan 
34. South Sudan Law Society, South Sudan  
35. Tanzania Human Rights Defenders Coalition, Tanzania 
36. Twerwaneho Listeners Club (TLC), Uganda 
37. Union de Jeunes pour la Paix et le Développement, Burundi  
38. WAN-IFRA (The World Association of Newspapers and News Publishers)  
39. West African Human Rights Defenders Network (ROADDH/ WAHRDN), West Africa
40. Zambia Council for Social Development (ZCSD), Zambia
41. Zimbabwe Human Rights NGO Forum, Zimbabwe

Published in ዜና

ባለፈው ሳምንት አርብ በታላቁ አንዋር መስጊድ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያነሱትን ተቃውሞ ተከትሎ በፖሊስ የታሰሩ የእምነቱ ተከታዮች፣ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ፍ/ቤት ቀርበው ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው።
የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሃመድ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ም/ቤት አባል ወ/ሪት ወይንሸት ሞላና የእስልምና እምነት ተከታዮች ከትናንት በስቲያ ረፋዱ ላይ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የቂርቆስ ክ/ከተማ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በመጠየቁ ፍ/ቤቱ ለመጪው ሐሙስ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
አዚዛ መሐመድ ባለፈው አርብ ስራዋን ለማከናወን በታላቁ አንዋር መስጊድ አካባቢ መገኘቷን የጠቆሙት የስራ ባልደረቦቿ፤ እስካሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለችና ለምን እንደታሰረች ለማወቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ም/ቤት አባል ወ/ሪት ወይንሸት ሞላ ተቃውሞው በተነሳበት ዕለት በደረሰባት ድብደባ እጇ የተጎዳ ሲሆን ወደ ፍ/ቤት ስትመጣ እጇ በፋሻ ተጠቅልሎ ታይታለች፡፡
ባለፈው አርብ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ለጁምዓ ስግደት ወደ ታላቁ አንዋር መስጊድ የሄዱ የእምነቱ ተከታዮች፤ “የታሰሩ ወገኖቻችን ይፈቱ”፣ “መብታችን ይከበር” እና ሌሎች  መፈክሮችን በማሰማት ጠንከር ያለ ተቃውሞ የገለፁ ሲሆን ድብደባ ከደረሰባቸው ሰዎች በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የእምነቱ ተከታዮች መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ ፖሊስ ለተቃውሞው መንስኤ ይሆናሉ ብሎ የጠረጠራቸውን በእስር ያቆየ ሲሆን ሌሎቹ በዚያኑ ዕለት ሌሊትና በነጋታው መፈታታቸው ተዘግቧል፡፡  

Published in ዜና

“በደህንነቶች የሚደርስብኝን ጫና መቋቋም አልቻልኩም”

    በ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ላይ ከሪፖርተርነት እስከ ከፍተኛ አዘጋጅነት ድረስ የሰራውና በቅርቡ የተመሰረተው “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ አገር ጥሎ ተሰደደ፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት ጀምሮ የደህንነት ኃይሎች ሲያደርጉበት የነበረውን ክትትል ተቋቁሞ ስራውን ሲሰራ እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፤ ዘንድሮ ከጥቅምት ወር ጀምሮ አዲስ በተመሰረተው የጋዜጠኞች ማህበር (ኢጋመ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ ከተመረጠ በኋላ ግን የደህንነቶቹ ክትትልና ወከባ እረፍት እንደነሳው ተናግረዋል፡፡ የማህበሩን መመስረት አስመልክቶ ከማህበሩ ፕሬዚዳንት ከጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ ጋር ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ቃለ-ምልልስ ከሰጠ በኋላ በደህንነት ሰዎች መዋከቡ እንደተባባሰ የገለፁት ምንጮች፤እነዚሁ ደህንነቶች የሚሰራበት ተቋም ድረስ በመሄድ ስለማህበሩ መረጃ እንዲሰጥ አሊያም ማህበሩን እንዲለቅ ማስጠንቀቂያ እንደሰጡትና በዚህም ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ከማህበሩ ለመራቅ መገደዱን ጠቁመዋል፡፡
ዘንድሮ በመጋቢት ወር ላይ በኬኒያ ናይሮቢ ለጋዜጠኞች በተዘጋጀ ስልጠና ላይ ተካፍሎ ከተመለሰ በኋላ ከሌሎች የኢጋመ አመራር አባላት ጋር በ “አርቲክል 19” የሰለጠነ በማስመሰል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሽብርተኝነት ከተወነጀሉት መካከል አንዱ ሆኖ መውጣቱ ስጋቱን ይበልጥ እንዳባባሰበት የገለፁት ምንጮች፤ በደረሰበት ከፍተኛ ጫናም ለአጭር ጊዜ ከማህበሩ ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋርጦ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ ደግሞ ማህበሩ ያካሄደውን ውይይት ተከትሎ የማያውቃቸው ሰዎች  “በዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ላይ እንድትመሰክር እናደርጋለን፤ ካልሆነም መታሰረህ አይቀርም” በሚል እንዳስፈራሩት ምንጮች ጠቁመው፤ በዚህም የተነሳ አገሩን ጥሎ መሰደዱን ገልፀዋል፡፡
የጋዜጠኛ ዘሪሁንን መሰደድ በተመለከተ ያነጋገርነው የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፍሬው አበበ፤ ጋዜጠኛው መሰደዱንም ሆነ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ እንደማያውቅ ጠቁሞ፤ ከ10 ቀን በላይ በስራ ገበታው ላይ ባለመገኘቱና ስልኩ ዝግ በመሆኑ፤ ወደ ስራ ገበታው እንዲመለስ የሚገልጽ ደብዳቤ በዝግጅት ክፍሉ መለጠፉን ተናግሯል፡፡
ጋዜጠኛ ዘሪሁን ምንም ሳይናገር አድራሻውን በመሰወሩ፣ ሲጨነቁ መሰንበታቸውን ዋና አዘጋጁና የሥራ ባልደረቦቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና

በ30 ሚ.ብር ካፒታል የሚቋቋመው ኩባንያ በአንድ ዓመት ውስጥ ሥራ ይጀምራል\

   ሆላንዳውያን ባለሃብቶች አዲስ የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ለማቋቋም የፕሮጀክት አዋጪነት ጥናት እያከናወኑ እንደሆነ ተገለፀ፡፡
አዲሱ የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያ ቀድሞ በሆላንድ መንግስት ድጋፍ ተቋቁሞ የነበረውን “ሆላንድ ካር” ይተካል የተባለ ሲሆን አዲሱ ኩባንያ ከ“ሆላንድ ካር” ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ጥናቱን ለማካሄድ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ሚስተር ኤሪክ ትሪዎሽቻ ቫን ስቺሊቲንጋ ተናግረዋል፡፡
ሚስተር ስቺሊቲንጋ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ አዲሱ ኩባንያ “ኢትዮ-ደች ሞተርስ ካምፓኒ” በ30 ሚሊዮን ብር ካፒታል በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተቋቁሞ ከቀድሞ የተሻሉና ጥራት ያላቸው አዳዲስ ሞዴል የቤት አውቶሞቢሎችን እየገጣጠመ ለገበያ ያቀርባል ብለዋል፡፡ ከሚያካሂዱት የፕሮጀክት አዋጭነት ጥናት ጐን ለጐን ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር በኩባንያው ዙሪያ ውይይት እያደረጉ መሆኑን የጠቆሙት ሚስተር ስቺሊቲንጋ፤ መንግስት በቅርቡ ለመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያዎች የታክስ ማሻሻያ ማድረጉ በሆላንድ መንግስት የሚደገፉ ሆላንዳውያን ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪው እንዲገቡ እንደገፋፋቸው ተናግረዋል።
የቀድሞውን “ሆላንድ ካር” እና አዲሱን “ኢትዮ-ደች ሞተርስ” የሚያመሳስላቸው ሁለቱም በሆላንድ መንግስት በጎ ፍቃደኝነት የተቋቋሙ መሆናቸው ብቻ ነው ያሉት ሚስተር ስቺሊቲንጋ፤ አዲሱ ኩባንያ ሆላንዳውያን በኢትዮጵያ የመኪና ኢንዱስትሪ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ አጠናክሮ ለመቀጠል ታስቦ የሚቋቋም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ለአዲሱ ኩባንያ ጥሬ እቃ እንዲያቀርብ ከቻይናው ጄኤሲ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም ሚ/ር ስቺሊቲንጋ አክለው ገልጸዋል፡፡  

Published in ዜና

     የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ከ “ጤና ለሁሉም ዘመቻ” ጋር በመተባበር ባዘጋጀው “የጤና መድህንን ለህዝብ የማስተዋወቅ ዘመቻ” አገር አቀፍ የዘገባ ውድድር ያሸነፉ ጋዜጠኞችን ከትናንት በስቲያ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባከናወነው ስነስርዓት ሸለመ፡፡
የህትመት፣ የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮና የድረ-ገጽ በሚሉ አራት ምድቦች በተከፋፈለውና ጋዜጠኞች የማህበራዊ ጤና መድህንን በተመለከተ ለአንባቢ፣ ለተመልካችና ለአድማጭ ያቀረቧቸውን ዘገባዎች ለውድድር ባቀረቡበት በዚህ ውድድር ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡ አሸናፊዎች ከኤጀንሲው ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ከዶ/ር መንግስቱ በቀለ እጅ የላፕቶፕ፣ የዘመናዊ ሞባይል ቀፎ፣ የፎቶግራፍ ካሜራና የሰርተፍኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ዶ/ር መንግስቱ ሽልማቱን ለአሸናፊዎች ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ ጋዜጠኞች፣ የድረ-ገጽ ጸሃፊያንና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር  ኤጀንሲው ለያዘው ዕቅድ መሳካት ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅሰው፣ ኤጀንሲው በቀጣይም መሰል ስራዎችን በቅንጅት መስራቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የ “ጤና ለሁሉም ዘመቻ” ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይወት እምሻው በበኩላቸው፣ የጤና መድህን በገንዘብ እጦት ምክንያት ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ተቸግረው በህመም ለሚሰቃዩና ለሞት ለሚዳረጉ ዜጎች ትልቅ መፍትሄ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የጤና መድህን ስርዓትን በተመለከተ በህብረተሰቡ ውስጥ በቂ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ብዙ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመው፣ በዕለቱ ለሽልማት የበቁትም ሆኑ ሌሎች ጋዜጠኞች ስርዓቱን ለመዘርጋት በሚደረገው ቀጣይ እንቅስቃሴ ውስጥም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳይ ቢሮና ከብሮድካስት ባለስልጣን የተውጣጡ የውድድሩ ዳኞች ባካሄዱት ግምገማ፤ በህትመት ዘርፍ መላኩ ብርሃኑ ከአዲስ ጉዳይ መጽሄት፣ ምህረት አስቻለው ከሪፖርተር ጋዜጣ፣ ስመኝ ግዛው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት ተሸልመዋል፡፡
በድረ-ገጽ ዘርፍ ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው፣ ጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ፣ ጋዜጠኛ ኢዮብ ካሣ ሲያሸንፉ፤ በሬዲዮ ዘርፍ ጋዜጠኛ ገዛኸኝ ተስፋዬ እና ጋዜጠኛ ገናናው ለማ ከደቡብ ክልል መገናኛ ብዙሃን፣ ጋዜጠኛ ገመቺስ ምህረቴ ከፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት፤ በቴሌቪዥን ዘርፍ ደግሞ ጋዜጠኛ ሰለሞን ገዳ በብቸኝነት አሸናፊ ሆኗል፡፡

Published in ዜና

   የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች በጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የምክር ቤቱና የኡላማ ምክር ቤት አባላት “መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ መርጃ ማዕከል”ን በመጎብኘት ከ100 ሺ ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁሶችን ለገሱ፡፡
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ኪያር ሼህ መሃመድ አማን፣ የኡላማ ምክር ቤት ፀሃፊ ሼክ ዚአዲን ሼህ አብዲላዚዝን  ጨምሮ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ከትናንት በስቲያ ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት አልባሳት፣ የገላ ሳሙና፣ ዳይፐርና ሶፍት የመሳሰሉ መገልገያ ቁሳቁሶችን ለግሰዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር፤ የማዕከሉ እንቅስቃሴና ተግባር ከጠበቁትና ከገመቱት በላይ መሆኑን ገልፀው “መቄዶንያ በየጎዳናው የወደቁትን አንስቶ ለክብር በማብቃቱ ትልቅ ባለውለታ ነው፣ ይህን ስራውን ሁላችንም መደገፍ በጎ ተግባሩን ለሃገር ብቻ ሳይሆን ለዓለም ማስተላለፍ አለብን” ብለዋል፡፡
ተቋሙ ከአዲስ አበባ ውጪም ቅርንጫፍ ማዕከላት እንዲከፍት ምክር የለገሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ሙስሊሙ ህብረተሰብ መቄዶንያን ማስታወስ አለበት ብለዋል፡፡ ማዕከሉንም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲጎበኘው ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Published in ዜና

    የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ በተናጥል በቀረቡባቸው ክሶች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን የመስማት ሂደት በመጪው ሳምንት በጊዜ መጣበብ ምክንያት ሊካሄድ የማይችል ከሆነ ለመጪው ዓመት ይተላለፋል በማለት ፍ/ቤቱ መደበኛ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ ከትናንት በስቲያ ሀሙስ በጠዋት ክፍለ ጊዜው የአቃቤ ህግን አንድ ምስክር ካስደመጠ በኋላ፣ በሰጠው ትዕዛዝ በአቶ መላኩ ላይ በቀረቡ ቀሪ ክሶች ላይ ምስክሮችን ለመስማት የሚያስችል ጊዜ በመጪው ሣምንት ስለመኖሩ አቃቤ ህጎች በፅ/ቤት በኩል ጠይቀው እንዲረዱ፣ ካልሆነም ጉዳዩ ወደ ቀጣይ ዓመት ተሸጋግሮ ከጥቅምት 24-27 ምስክሮች በተከታታይ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ምስክር የጉምሩክና ገቢዎች መ/ቤት ሠራተኛ ሲሆኑ “ያማቶ ኢትዮጵያ” የተባለው ድርጅት ላስገባው እቃ ቀረጥ ስለመክፈሉ እንዲያጣሩ በመስሪያ ቤታቸው በኩል የስራ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እንደነበር በመግለጽ ነው ምስክርነት መስጠት የጀመሩት፡፡ የማጣራት ሂደቱን ሲያከናውኑም ኩባንያው ከተቋቋመበት 1996 እስከ 2001 ዓ.ም ጀምሮ የሉዲ ቀለምን በብቸኝነት ወደ ሃገር ውስጥ አስገብቶ ለሶስት ግለሰቦች ያከፋፍል እንደነበር፣ ይህን ሲያደርግም ሽያጩን ያለ “ቲን ነምበር” እንደሚያከናውን እንዲሁም የሶስቱ ነጋዴዎች አድራሻን መዝግቦ አለመያዙ እንደተደረሰበት፣ የኩባንያው ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ኢብራሂም “ለምን ያለ ቲን ነምበር ትሸጣላችሁ?” ተብለው ሲጠየቁ “አናውቅም ነበር፤ ለወደፊት እናዘጋጃለን” በማለት በራሳቸው ሳይሆን በሚስታቸው ስም “ቲን ነበር” አውጥተው ሽያጭ ማከናወን እንደጀመሩ አብራርቷል፡፡
በምርመራው ወቅትም ሉዲ ቀለምን ከ “ያማቶ ኢትዮጵያ” የሚረከቡት የሶስቱ ነጋዴዎች የባንክ ሂሳብ አቶ ሙደሰር ጢሃ በተባሉት አንደኛው ነጋዴ የሚንቀሳቀስና እቃዎቹን ከ “ያማቶ” ተረክበው በአንድ መጋዘን እንደሚያከማቹ እንደተደረሰበት ምስክሩ አስረድተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪም አድራሻና “ቲን ነበር” የሌላቸው እስከ 200 ሺህ ብር ግብይት የተፈጸመባቸው ደረሰኞች መገኘታቸውን ምስክሩ አስረድተዋል፡፡
ምስክሩ ከተከሳሽ ጠበቆች የቀረቡላቸውን መስቀለኛ ጥያቄዎችና የፍ/ቤቱን የማጣሪያ ጥያቄ ከመለሱ በኋላ ፍ/ቤቱ ከላይ የተመለከተውን ትዕዛዝ ሰጥቶ የግማሽ ቀኑ ችሎት ተዘግቷል፡፡

Published in ዜና

          በኢትዮጵያ የባንክ ታሪክ ለገንዘብ አስቀማጮች በየወሩ ወለድ በመክፈል፣ የውድ እቃዎችና ሰነዶች ማስቀመጫ ሳጥን አገልግሎት፣ የቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሂሳቦችን በጥምረት በማንቀሳቀሰና ልዩ የቁጠባ ሂሳብ በመክፈት ፈር ቀዳጅ የሆነው አቢሲኒያ ባንክ፤ ሰሞኑን የተንቀሳቃሽ ስልክ፣ የካርድና የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ የባንክ አገልግሎት መጀመሩን ገልጿል፡፡
ትናንት ረፋድ ላዩ በጊዮን ሆቴል የባንኩ ኃላፊዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳብራሩት፤ በተንቀሳቃሽ ስልክ የግል ሂሳብ እንቅስቃሴ ማወቅ፣ ከአንድ ሂሳብ ወደ ሌላው ገንዘብ ማስተላለፍ፣ የተለያዩ ክፍያዎችንና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችን በባንኩ ማግኘት ይቻላል፡፡

በካርድ የባንክ አገልግሎት ደግሞ ገንዘብ ማውጣት፣ የባንክ እንቅስቃሴዎችን መግለጫ ማግኘት፣ ያለውን ሂሳብ ማወቅ፣ ገንዘብ መላክና መቀበል እንዲሁም የአገልግሎት ክፍያ መክፈልና መሰል አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚቻል  ታውቋል፡፡ ካርዱ “ሐበሻ ካርድ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ካርዱ የኤቲኤም ማሽኖች ባሉባቸው የንግድ ማዕከሎች በዓላትን ጨምሮ የ24 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
ባንኩ “በኤቲ ኤም” እና “ፖስ” (ፖይንት ኦቭ ሴል ማሽን) የተገለፁትንና መሰል አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስችሉ ሶስት አይነት ኤሌክትሮኒካል ካርዶች ማዘጋጀቱን የገለፁት ኃላፊዎቹ፤ “ሐበሻ ጎልድ ካርድ”፣ “ሐበሻ ዴቢት ካርድ” እና “ሐበሻ ፕሪፔይድ ካርድ” በመባል እንደተሰየሙ ጠቁመዋል፡፡
በሁሉም ካርዶቹ ገንዘብ ከኤቲኤም ለማውጣት ትንሹ የገንዘብ መጠን 50 ብር ሲሆን ከፍተኛው በሀበሻ ጎልድ ካርድ 15 ሺ፣ በሃበሻ ዴቢት ካርድ 10 ሺ እንዲሁም በሃበሻ ካርድ አራት ሺ ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡
ቅርንጫፎቹ 102 የደረሱትና 2,800 ሰራተኞች ያሉት አቢሲኒያ ባንክ፤ 50 ያህል የኤቲኤም ማሽኖችን በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች የተከለ ሲሆን፣ ወደ 200 የሚደርሹ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖችን በአዲስ አበባ በሚገኙ የገበያ ማዕከላት እያሰራጨ እንደሚገኝ የባንኩ ኃላፊዎች ገልፀዋል፡፡  

Published in ዜና

ተቃዋሚዎች በአተገባበሩ ላይ ብሔራዊ መግባባት መፈጠር አለበት ይላሉ
የፀረ-ሽብር ህጉ የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ መውጣቱን ተከትሎ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና  ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት ተከሰው መታሰራቸው በህጉ ላይ የከረረ ተቃውሞ የሚሰነዝሩ ወገኖች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡ አንድነት ፓርቲ መቃወም ብቻም ሳይሆን ህጉ ከእነአካቴው እንዲሰረዝ “የሚሊዮን ድምፆች ለነፃነት” በሚል ባደረገው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ፣ ያቀደውን ያህል ድምፅ ማግኘቱን ጠቁሞ  ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው መግለፁ አይዘነጋም፡፡
የፀረ-ሽብር ህጉ አወዛጋቢነት በአገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፤የፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች መታሰርን በመቃወም መንግስት ህጉን፣ተቺዎቹን ለማጥቂያነት እየተጠቀመበት ነው በማለት ይኮንናሉ፡፡   
 የግንቦት 7 ዋና ፀሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የመን ላይ ተይዘው ለኢትዮጵያ መንግስት መተላለፋቸውን ተከትሎ አራት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት ተይዘው መታሰራቸው (በሽብርተኝነት የተከሰሱትን  ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች ጨምሮ) በብዙዎች ዘንድ ስጋትን ፈጥሯል፡፡ ፓርቲዎቹም የፖለቲከኞቹን መታሰር  በመቃወም መግለጫዎች አውጥተዋል፡፡ ለመሆኑ በሽብር ወንጀል እየተጠረጠሩ የሚታሰሩ ዜጐች መበራከት በአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ምን አንደምታ ይኖረው ይሆን? በቀጣይስ ሀገሪቷን ወዴት ይመራታል? በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የፓርቲ አመራሮችና የህግ ባለሙያዎች የሰጡንን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡


“በኢትዮጵያ ሽብርተኛ ማለት ነፃነትን መሻት፣ እውነትን መፈለግ ነው”
(ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

ሽብርና ሽብርተኝነት አሁን በኢትዮጵያ ባለው ግንዛቤ፤ እውነት ለሚናገሩ፣ለህብረተሰቡ መብት መከበር ለሚቆሙ፣ መንግስትን አምርረው ለሚተቹ ሰዎች የሚሰጥ ስም ነው፡፡ በየጊዜው ሽብርተኛ እየተባሉ የሚታሠሩት የማህበረሰብ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ መሪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሽብርተኛ ማለት  ነፃነትን መሻት፣ እውነትን መፈለግና  መንግስትን መተቸት ሆኗል፡፡
መንግስት ሰዎችን በብዛት ማሰሩ አቅመቢስ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል፡፡ የህዝብ ጥያቄ እያሸነፈ መንግስት  ተቀባይነት እያጣ ሲመጣ ነው ሁሉን ነገር በጉልበት ለማድረግ የሚፈልገው፡፡ በአንፃሩ እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች በታሰሩ ቁጥር የነፃነት ትግሉ እየተፋፋመ እንደሆነ ነው የሚያሳየው፡፡ በዚህ ረገድ እኔ ብሩህ ተስፋ ይታየኛል፡፡ ምክንያቱም ለእውነት ብለው ለመታሰር የሚደፍሩ ሰዎች (እነ አንዷለም ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ) እየበዙ ነው፡፡ ለመታሰር ዝግጁ የሆኑ ሰዎች በዙ ማለት ወደ ለውጥ መቅረባችንን ያመለክተናል፡፡


አዋጁ በአግባቡ እየተተረጐመ አይደለም”
ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ የኢዴፓ ሊቀመንበር)


በአጠቃላይ መንግስት እየተከተለ ያለው አካሄድ ለዲሞክራሲ ግንባታው በጣም እንቅፋት እየፈጠረ ነው፡፡ በተለይ የፀረ ሽብር አዋጅን በተመለከተ የአተረጓጐም ስህተት እየተከተለ ነው የሚል ግንዛቤ አለን፡፡
የፀረ ሽብር ህግ ቢያስፈልገንም አተረጓጐሙ ግን በአግባቡ መሄድ አለበት፡፡ መንግስት የራሱን ጥቅም ለማስከበርና የገዥውን ፓርቲ እድሜ ለማራዘም ብቻ የተናገረውንም፣ ጦር ይዤ እታገላለሁ የሚለውንም፣ የሚጽፍበትንም--- በአጠቃላይ ገዥውን ፓርቲ የማይደግፈውን  ሁሉ በሽብር ስም ማሠሩ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡
ይሄ አጠቃላይ የዲሞክራሲ ሂደቱን የሚያስተጓጉል ሲሆን የህብረተሰቡንም መብት የሚጫን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹንም አካሄድ ሊያበላሽ የሚችል፤ ወደ ኋላ እየመለሰን ያለ አካሄድ እንደሆነ ኢዴፓ ያምናል፡፡
ከዚህ አንፃር ገዥው ፓርቲ፣ ለዲሞክራሲ ግንባታ ምንም አይነት ቁርጠኝነት እያሳየ አለመሆኑን እንዲሁም  የስርአት ለውጥ በተጨባጭ ከምርጫ ሳጥን እንዳይገኝ፣ መጪውን ምርጫ ለማበላሸት እየተከተለው ያለው መንገድ ነው ብለን እናምናለን፡፡
የኛ ፓርቲ ብሔራዊ መግባባትን እንደ አንድ ትልቅ አጀንዳ ይዞ ይንቀሳቀሳል፡፡ መንግስት ብሔራዊ መግባባት መፈጠር አለበት ሲባል “የተጣላ ሰው የለም፤ማንን ከማን ለማግባባት ነው” የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ቆም ብሎ በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰብ አለበት፡፡ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶች መንግስትን ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የምንጠይቅበትን አካሄድ በጋራ መፈለግ ይገባናል። አለበለዚያ ለህዝባችን ምንም ነገር ሳንሰራ፣ የቆምንለትን አላማ ሳናሳካ እንዲሁ ዝም ብለን ጊዜ መፍጀት ይሆናል፡፡
በፀረ ሽብር ህጉም ላይ ቢሆን የጋራ ግንዛቤና መግባባት መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ህጉ በጣም አስፈላጊ ነው፤ በአተረጓጐሙ ዙሪያ ግን የጋራ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ ሲረቀቅ ጀምረን እስካሁን በአተረጓጐሙ ላይ ተቃውሟችንን ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ በህጉ አተረጓጐም ላይ የጋራ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተቃራኒ ሃሳብን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደውም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ቁጭ ብለን መግባባት ይኖርብናል፡፡


 “ሽብርተኛ ስለመሆናቸው መንግስት ተጨባጭ ማስረጃ አያቀርብም”

(አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ የመድረክ አመራር)


በሠላማዊ ትግሉና ሠላማዊ ታጋዮች ላይ በሽብርተኝነት ስም የሚወሰዱት እርምጃዎች፣ሽብርተኝነት የሚለውን ስያሜ በአግባቡ እንዳንረዳ እያደረገን ነው ያለው፡፡ ሽብርተኝነት ሲባል በአለማቀፍ ደረጃ የታወቁ ነገሮች አሉ፡፡ አሸባሪዎች በሃይል አስፈራርተው የራሳቸውን ፖሊሲና አማራጭ ሌላው እንዲከተል በማድረግ፣ “ይሄን ባታደርግ እንዲህ አደርጋለሁ” የሚሉ ናቸው፡፡ መድረክም ይህን መሰሉን ድርጊት አጥብቆ ይቃወማል፡፡ አሁን በኛ ሀገር እነዚህ አሸባሪ ተብለው የሚወነጀሉ ሰዎች ይሄንን አድርገዋል ወይ? ማንን ነው ያስገደዱት? ማንን ነው ያስፈራሩት? በማን ላይ ነው እርምጃ የወሰዱት? በሚለው ላይ መንግስት በተጨባጭ ማስረጃ አያቀርብም፡፡ በዚህም ሳቢያ እኛም አሸባሪ ስለመሆናቸው ምንም ልንገነዘብ አልቻልንም፡፡ ጭራሽ አሸባሪ በሚለው ጉዳይ ላይ ግራ እንድንጋባ እየሆንን ነው፡፡ ሽብርተኝነት የሚለው በራሱ ግልጽነት ይጐድለዋል፡፡
መንግስት የሽብርተኝነትን ትርጓሜ ጥርት አድርጐ ባለማስቀመጡ፣ ህጉን ሠላማዊ ሰዎችን ለማስፈራሪያነት እየተጠቀመበት ነው የሚል ስጋት አለን፡፡ የሽብር ክሶችና እስራት እየተጠናከረ መቀጠሉ ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ፤ ለማሸማቀቅና የፍርሃት ድባብን ህዝብ ላይ ለመጫን ነው፡፡ ህዝብ በፍርሃትና በመሸማቀቅ የተሣተፈበት ምርጫ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊሆን አይችልም። ሰው ተደፋፍሮ ከውስጡ መሸማቀቅና ፍራቻን እንዲያስወግድ ከተፈለገ፣ አሸባሪን ከሰላማዊ ትግል የሚለይ ነገር መቀመጥ አለበት፡፡ አለበለዚያ አሁን የተያዘው የሽብርተኝነት ግንዛቤ በምርጫም ሆነ በፖለቲካ ሠላማዊ ትግል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ ግንዛቤውን ለማጥራትም ሆነ ችግሩን ለመፍታት ብሔራዊ መግባባት ያስፈልገናል። ሽብርተኝነት ምንድን ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ብሔራዊ መግባባት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሽብርተኝነትን እንዴት በጋራ እንታገል በሚለው ላይም በተመሳሳይ የጋራ መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ ብሔራዊ መግባባት ካለ የሽብር አደጋዎችን ሁሉ መከላከል እንችላለን፡፡ ገዥው ፓርቲ የውይይት በሮችን ሁሉ መዝጋቱን ትቶ፣ ተቃዋሚዎችን እንደጠላት መመልከቱን አቁሞ፣ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበትን የውይይት መድረክ ሊያመቻች  ይገባዋል፡፡

===========
“አዋጁ የምርጫ 97 ውጤት ነው”
(ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፤ የአንድነት ሊቀመንበር)

ፓርቲዬ አንድነት የፀረ - ሽብር አዋጁ፤ የዲሞክራሲ ሂደቱን የማፈን ጥረት ውጤት ነው ብሎ ያምናል፡፡ በዚህ መሠረት በ“የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት” ላይ በዋናነት የፀረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ ጠይቀናል፡፡ ህጉ ከየት መጣ ብለን ከጠየቅን፣የምርጫ 97 ውጤት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኢህአዴግ በነፃ ምርጫ ማሸነፍ እንደማይችል ሲረዳ፣ የዲሞክራሲ ተቋማትን የማፈን እንቅስቃሴ ውስጥ ነው የገባው፡፡ ሚዲያዎችን፣ ፓርቲዎችን፣ሲቪል ማህበራትን ማፈን የሚለውን እንደ አማራጭ ለመጠቀም ስለፈለገ፣ በእያንዳንዱ ጉዳይ አዋጅ አውጥቶበታል፡፡ ስለዚህ የፀረ ሽብር ህጉም የዲሞክራሲ ስርአቱን ሙሉ ለሙሉ ለማዳፈን የወጣ ነው ብለን እናምናለን፡፡
እኛ የፀረ ሽብር ህጉ መሠረዝ አለበት ስንል፣ ሽብርተኝነትን እንደግፋለን ማለት አይደለም፡፡ ከማንም በላይ ሽብር ለሃገራችን አስጊ ነው በሚል እምነት፣ ፓርቲዬም ሆነ እኔ ከመንግስት ጐን ተሠልፈን የምንዋጋው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን  ያለው አዋጅ እየተተረጐመበት ባለው አግባብ ላይ ከፍተኛ ጥያቄ አለን፡፡
ሚዲያው አካባቢ ሲኬድ በከፍተኛ ሁኔታ ራሱን በራሱ የሚገድብ (Self censorship) ሆኗል። ሲቪል ሶሳይቲውም የኢህአዴግን ቡራኬ ካላገኘ መኖር አይችልም፡፡ ይሄ ዲሞክራሲውን በእጅጉ ይጐዳል፡፡
ኢህአዴግ ኳሱ በእጁ ነው፡፡ ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ የሆነ ቦታ መቆማቸውም አይቀርም፡፡
ስለዚህ ዲሞክራሲው እንዳይቀጭጭ፣ እንዳይጐዳ ኳሱን በእጁ የያዘው ኢህአዴግ ቆም ብሎ ማሰብ ይኖርበታል፡፡ የዲሞክራሲ ሂደቱ በሚፈቅደው መጠንም ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ መድረኩንም መፍጠር አለበት፡፡ እኛ በዚህ አዋጅ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በፍትህና በዲሞክራሲያዊ ስርአቱ ላይ ከብሔራዊ መግባባት የሚያደርስ ውይይት እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ ብሔራዊ መግባባት መኖር አለበት፡፡   


“ህጉ ለኛ አስፈላጊ ነው ወይ?”

(አቶ ተማም አባቡልጉ፤ ጠበቃና የህግ አማካሪ)

ብዙ ሰው ህጉ በአግባቡ መተርጐም አለበት በሚለው ላይ ነው ጥያቄ የሚያነሳው፡፡ እኔ ደግሞ ህጉ ለኛ አስፈላጊ ነው ወይ የሚለውን ነው የምጠይቀው፡፡ ህጉ ላይ የተጠቀሱት ነገሮች እኮ በወንጀለኛ ህጉ ላይ አሉ፡፡ እንደገና በሌላ መልክ መምጣታቸው አግባብ አልነበረም፡፡ በዚህ ጉዳይ የሚከሰሱ ሰዎችን ስንመለከት ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር “ህጉ ለማጥቂያነት አልዋለምን?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የሽብር አዋጅ በየትኛው ዓለም ቢሆን በአገር ላይ የሚደርስን ጥቃት  የሚከላከል እንጂ ፓርቲን፣ ጋዜጣንና ሃሳብን በነፃነት መግለጽን አይደለም መገደብ ያለበት፡፡ ለምሣሌ ሩዋንዳ በህጓ ላይ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን በተመለከተ፣ ቀጥታ የጅምላ ጭፍጨፋን የሚያነሳሱ ሃሳቦችን ለይታ ነው ገደብ ያበጀችው፡፡ የኛ ግን ጥቅል ነው፡፡ ይሄን አይመለከትም ተብሎ ተለይቶ መቀመጥ አለበት። በእንግሊዝ ሀገር ህጉ ሲወጣ ፖለቲከኞች “አንዴ ስልጣን ላይ የወጣው መንግስት ስልጣን እንዳይለቅ የማድረጊያ መንገድ ሆኗል” ብለው ነው ህጉን ኋላ ላይ ያስቀሩት፡፡ ስለዚህ በኛም ሃገር ህጉ ለፖለቲካ ማጥቂያ አይውልም ተብሎ አይታሰብም፡፡

  •      መንገደኞች በአውሮፕላን መጓዝ እየፈሩ ነው፣ ባለሙያዎች አደጋ ቀንሷል እያሉ ነው
  • የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በአመት 65 ሚ. ዶላር ይሰበስባሉ፣ በ5 ወር ብቻ 600 ሚ. ዶላር ካሳ ይከፍላሉ

            አመቱ ለአለማችን የአየር ትራንስፖርት የቸር አልሆነም - በተለይ ደግሞ ለማሌዢያ፡፡ ከወራት በፊት የማሌዢያ አየርመንገድ ቦይንግ 777 አውሮፕላን 239 ሰዎችን ይዞ ከኳላላምፑር ወደ ቤጂንግ በመብረር ላይ ሳለ፣ ድንገት ከራዳር እይታ ውጭ ሆነ፡፡ አለም ድንገት ደብዛው የጠፋውን አውሮፕላን ፍለጋ ውቅያኖስ አሰሰ፤ ከወዲያ ወዲህ ተራወጠ፤ ወደ ሰማይ አንጋጠጠ፡፡ ከዛሬ ነገ ይገኛል በሚል ተስፋ ፍለጋው ለወራት ዘለቀ - ተስፋ እንደራቀ፡፡ አንዳች እንኳን ተጨባጭ መረጃ ሳይገኝ፤ አውሮፕላኑን የበላው ጅብ ሳይጮህ፣ ነገሩ እንቆቅልሽ እንደሆነ ዘለቀ፡፡ ማሌዢያ በላይዋ ላይ የደረበችውን ማቅ ሳታወልቅ፣ ያለፈው ሃዘን ሳይወጣላት፣ በሆነው ነገር ሳትጽናና ሌላ ነገር ሆነ - ሌላ አውሮፕላኗ በአሰቃቂ ሁኔታ ተከሰከሰ፡፡ ይህ ክስተት ለማሌዢያ ብቻም ሳይሆን ለአጠቃላዩ የአቪየሽን ኢንዱስትሪና ለመላው አለም አስደንጋጭ መርዶ ነበር፡፡

የማሊዢያው አየር መንገድ አውሮፕላን ከቀናት በፊት በበረራ ቁጥር ኤም ኤች 17 ከአምስተርዳም ተነስቶ ወደ ኳላላምፑር በመጓዝ ላይ እያለ፣ ዩክሬንንና ሩስያን በሚያዋስነው ድንበር ላይ በሚሳዬል ተመትቶ መውደቁንና 298 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የአየር ክልል ውስጥ መብረር ወይም አለመብረር የዓለማችን ታላላቅ አየር መንገዶች ዋነኛ ጥያቄና ጭንቀት ሆኗል፡፡ ብዙዎቹ አለማቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ተቆጣጣሪዎች በዚህ የግጭት አካባቢ በረራ እንዳያደርጉ በአየርመንገዶች ላይ እገዳ ባለመጣላቸው ወይም ማስጠንቀቂያ ባለመስጠታቸው፤ አብዛኛዎቹ አየርመንገዶች የአየር ክልሉን በማቋረጥ ከአውሮፓ ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ መጓዛቸውን ቀጥለው ነበር፡፡ በአካባቢው የተቀሰቀሰው ግጭት ስጋት ያጫረባቸው ኤር በርሊን፣ ኮሪያን ኤርና ኤር ስፔስን የመሳሰሉ የተለያዩ አገራት አየር መንገዶች ግን፣ ወደዚህ አየር ክልል ድርሽ ማለት ካቆሙና ዙሪያ ጥምጥም መብረር ከጀመሩ ወራት አልፏቸዋል፡፡ “መሰል ግጭቶች ያሉባቸው አካባቢዎች ለአየር መንገዶችና ለአጠቃላዩ የአለማችን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ስጋት ሆነዋል፡፡

እኛም ስጋት ስለገባን በተቻለን መጠን ከአካባቢዎቹ ስንርቅ ቆይተናል፡፡ ከግጭት አካባቢዎች ለመሸሽ የበረራ መስመሮችን መቀየር፣ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉ አይቀሬ ነው። አየር መንገዳችን ግን፣ ለደህንነት ሲል ተጨማሪ ወጪ ሲያወጣ ነው የቆየው” ብለዋል የኤዥያና አየር መንገድ ቃል አቀባይ፡፡ የማሌዢያ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሊሎ ቲዮንግ የአገራቸው አውሮፕላን ከሰሞኑ አደጋ ላይ መውደቁን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ለምን በአደገኛ አየር ክልል ውስጥ በረረ በሚል የተሰነዘረበትን ትችት አልተቀበሉትም፡፡ “ይህን የአየር ክልል እያቋረጥን መጓዝ ከጀመርን አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ምንም የገጠመን ችግር አልነበረም፡፡ ደህንነቱ የተረጋገጠ ክልል ነው፡፡ ሌሎች አየር መንገዶችም ይሄን ክልል እያቋረጡ መብረራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ታዲያ እኛ ለምንድን ነው የምናቆመው?” ሲሉ ጠይቀዋል ቲዮንግ፡፡ የማሌዢያው አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ኣለምን አሳዝኖ ሳያበቃ፣ ከቀናት በኋላም ሌላ አሳዛኝ ክስተት ተፈጠረ፡፡

በበረራ ቁጥር ጂ ኢ 222 በረራ ላይ እያለ ባጋጠመው አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ሳቢያ፣ በታይዋኗ የፔንጉ ደሴት ለማረፍ በመሞከር ላይ የነበረውና ንብረትነቱ የትራንስ ኤዥያ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላን ታይዋን አካባቢ ተከሰከሰ፡፡ 47 ሰዎችም ለህልፈተ ህይወት ተዳረጉ፡፡ የአቪየሽን ዘርፉ መርዶ አላበቃም፡፡ ባለፈው ረቡዕ ደግሞ ሌላ አሳዛኝ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ መርዶ ተሰማ፡፡ 116 ተሳፋሪዎችን ይዞ በበረራ ቁጥር ኤኤች 5017 ከቡርኪናፋሶ በመነሳት ወደ አልጀርስ በመጓዝ ላይ የነበረ ንብረትነቱ የኤር አልጀሪያ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን በአሰቃቂ ሁኔታ ተከሰከሰ፡፡ ቀጠለናም የታይዋን አየርመንገድ አውሮፕላን ተከስክሶ ከ50 በላይ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ተዳረጉ፡፡ እነዚህ ሰሞንኛ አሰቃቂ አደጋዎች፣ ብዙዎች የአቪየሽን ኢንዱስትሪውን እንዲጠራጠሩት አድርጓል ይላል ዩ ኤስ ቱዴይ፡፡ አደጋዎቹ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መከሰታቸውን በጥርጣሬ ያዩት እንዳሉ የጠቆመው ጋዜጣው፣ የኢንዱስትሪው ኤክስፐርቶች ግን ነገሩ ከሁኔታዎች መገጣጠም የዘለለ ትርጉም የለውም ስለማለታቸው ዘግቧል፡፡ “የማሌዢያው ተመትቶ፣ የትራንስ ኤዢያው ደግሞ በአየር ጠባይ ሳቢያ ነው አደጋ የደረሰባቸው። የሁለቱ አደጋዎች በተቀራራቢ ጊዜ መከሰት አጠቃላዩን ኢንዱስትሪ ስጋት ላይ የሚጥልም ሆነ፣ ተሳፋሪዎች የአውሮፕላን ጉዞ አደገኛ ነው ብለው እንዲደመድሙ የሚያስችላቸው አይደለም” ብለዋል በፍራንሲስኮ አትሞስፌር ምርምር ተቋም የጉዞ ተንታኝ የሆኑት ሄነሪ ሃርቲልት፡፡

ጆን ቤቲ የተባሉት የበረራ ደህንነት ፋውንዴሽን ፕሬዚደንትም ቢሆኑ፣ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው እንደተባለው ደህንነት የጎደለውና መንገደኞችን ስጋት ላይ የሚጥል፣ ሌላ አማራጭ እንዲወስዱ የሚያነሳሳበት ደረጃ ላይ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ “ባለፉት አስርት አመታት የአለማቀፉ የንግድ አቪየሽን ደህንነት እጅግ የሚገርም ደረጃ ላይ ደርሷል። አልፎ አልፎ መሰል አደጋዎች ሊፈጠሩ ቢችሉም፣ ክስተቶቹ የኢንዱስትሪውን አስተማማኝነት ጥያቄ ውስጥ አያስገቡትም። አደጋዎቹ አሳዛኝ ናቸው፤ የንግድ አቪየሽንም አሁንም ድረስ መቢገርም ሁኔታ ደህንነቱ የተረጋገጠ ነው!” ብለዋል ቤቲ፡፡ አመቱ ለአየር መንገዶች የመከራ ነበር የሚሉ ተበራክተዋል፡፡ የስታር ዶት ኮሙ ዘጋቢ ቫኔሳ ሉ ግን፣ ይህ አመት የአለማችን የንግድ አቪየሽን ከቀደምት አመታት የተሻለ ከአደጋ ነጻ የነበረበት ነው፡፡ የአለማቀፉ የአቪየሽን ደህንነት ኔትዎርክ ፕሬዚደንት ጠቅሶ ዘጋቢው እንዳለው፣ በዚህ አመት የተከሰቱ አደጋዎች ቁጥር ባለፉት አስር አመታት ከተከሰቱት አደጋዎች አማካይ ቁጥር በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ እርግጥ በአንድ አደጋ ለሞት የሚዳረጉ የአውሮፕላን ተሳፋሪዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡

በቅርቡ በተከሰከሱት ሁለቱ የማሌዢያ አውሮፕላኖች ብቻ 537 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ዘስታር ዶት ኮም እንደዘገበው፣ በዚህ አመት ብቻ በአለማችን 11 አሰቃቂ የአውሮፕላን አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ የአለማቀፉን የአየር ትራንስፖርት ማህበር መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፈው አመት በተከሰቱ መሰል 11 አደጋዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር 210 ነበር፡፡ ባለፈው አመት በአለማቀፍ ደረጃ ከ36 ሚሊዮን በላይ በረራዎች ተደርገው፣ ከ3 ቢሊዮን በላይ መንገደኞች ያለምንም አደጋ ካሰቡበት መድረሳቸቸውንም መረጃው ያስታውሳል። በመሆኑም የኢንዱስትሪው ደህንነት አደጋ ላይ ነው ብሎ ለመደምደም የሚያበቃ ምንም ነገር የለም፡፡ በቅርብ የተከሰተውን የማሌዢያው አየር መንገድ አደጋ ተከትሎ ስጋት ውስጥ የገቡት መንገደኞችና አየርመንገዶች ብቻም አይደሉም፡፡ የአውሮፕላን ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጭምርም እንጂ፡፡

ኒውዮርክ ታይምስ ከሰሞኑ እንደዘገበው፣ ለአየር መንገዶች የአደጋ ዋስትና የሚሰጡ ታላላቅ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተደጋጋሚ በሚከሰቱ አደጋዎች ሳቢያ የሚያወጡት ወጪ እየናረ በመምጣቱ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በጦርነት ቀጠናዎች አካባቢ ለሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖች ዋስትና የሚሰጡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡ የጦርነት አደጋ ዋስትና ደንበኞቻቸው ከሆኑ አየር መንገዶች በአመት በድምሩ 65 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ የሚሰበስቡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ በአውሮፕላኖች ላይ ለተከሰቱ አደጋዎች 600 ሚሊዮን ዶላር የካሳ ክፍያ መክፈላቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ኩባንያዎቹ ምን ያህል ለከፍተኛ ወጪ እንደተዳረጉና የኪሳራ ሰለባ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጧል፡፡ ተደጋግመው የሚሰሙት የአውሮፕላን አደጋዎች መንገደኞችን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል። ዘጋርዲያን ከትናንት በስቲያ ባስነበበው ጽሁፉ እንዳለው፣ ተደጋግመው የተከሰቱት የአውሮፕላን አደጋዎች አንዳንዶች ይህን የትራንስፖርት ዘርፍ በጥርጣሬና በስጋት እንዲያዩት አድርገዋቸዋል፡፡ በአውሮፕላን መጓዝ ለመሞት ፈቅዶ ትኬት መቁረጥ ነው ብለው ማሰብ የጀመሩ አልታጡም። ዘጋርዲያን ግን፣ ይህ ጅልነት ነው ይላል፡፡

የአለማቀፉን የሲቪል አቪየሽን ድርጅት መረጃ ጠቅሶ ዘጋርዲያን እንደጻፈው፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት በአለማቀፍ ደረጃ በተደረጉ በረራዎች የተከሰቱ አደጋዎች ሲሰሉ፣ ከ300 ሺህ በአንዱ ላይ ብቻ ነው አደጋ የተከሰተው፡፡ ይህም በአውሮፕላን አደጋ እሞት ይሆን የሚለው ስጋት ከንቱ መሆኑን ያሳያል ይላል ዘገባው፡፡ እንዲህ ያለ ስጋት የገባችሁ መንገደኞች፣ ከአደጋው ይልቅ ስጋቱ ይገላችኋል ያለው ዘጋርዲያን፣ ለዚህም የአሜሪካውን የመንትያ ህንጻዎች አደጋ በዋቢነት ይጠቅሳል፡፡ አደጋው በተከሰተ በቀጣዩ አመት በርካታ አሜሪካውያን አውሮፕላን ትተው መኪና ወደመጠቀም ዞሩ። የአውሮፕላን ተጠቃሚዎች ቁጥር እስከ 20 በመቶ ቀነሰ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ መኪና ተጠቃሚው በመብዛቱ መንገዶች ተጣበቡ፡፡ ረጅም ርቀት ማሽከርከር ታዲያ፣ ከአውሮፕላን የባሰ ለአደጋ የሚያጋልጥ አስጊ ነገር ወደመሆን ተሸጋገረ፡፡ በአቪየሽን መስክ ጥናት በማድረግ የሚታወቁትን ጀርመናዊ ፕሮፌሰር ገርድ ጊገንዘርን ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንደጠቆመው፣ በዚያው አመት በአገሪቱ በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በ1 ሺህ 595 ጭማሪ አሳየ፡፡ ቀስበቀስም አርም አውሮፕላን ብለው የነበሩ መንገደኞች ምርጫ በማጣት ፊታቸውን ወደ አውሮፕላን መልሰው አዞሩ፡፡

============

ባለፉት ሰባት ወራት በአለማችን የተከሰቱ የአቪየሽን አደጋዎች

ሃምሌ 24 የታይዋን አየር መንገድ አውሮፕላን ሃምሌ 23 የአልጀሪያ አየር መንገድ አውሮፕላን

ሃምሌ 23 የትራንስ ኤዥያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሃምሌ 17 የማሌዢያ አየር መንገድ አውሮፕላን

ሃምሌ 7 የቬትናም አየር ሃይል አውሮፕላን

ሃምሌ 5 በፖላንድ የግል አየር መንገድ አውሮፕላን

ሃምሌ 2 የስካይዋርድ ኢንተርናሽናል አቪየሽን አውሮፕላን ሰኔ 14 የዩክሬን አየር ሃይል አውሮፕላን

ግንቦት 31 የማሳቹሴትስ የግል ቻርተርድ አውሮፕላን ግንቦት 17 የላኦስ አየር ሃይል አውሮፕላን ግንቦት 8 የአሊሳና ኮሎምቢያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሚያዝያ 20 የሱሜን ኡርሂሊዩሊሜሊጃት አየር መንገድ አውሮፕላን ሚያዝያ 19 የሊኒያስ ኤሪያስ ኮመርሺያሌስ አየርመንገድ አውሮፕላን

ሚያዝያ 8 የሃጊላንድ አቪየሽን ሰርቪስስ አውሮፕላን

መጋቢት 28 የህንድ አየር ሃይል አውሮፕላን መጋቢት 22 የስካይዳይቭ ካቦልቸር አየርመንገድ አውሮፕላን

መጋቢት 18 የሄሊኮፕተርስ ኢንክ ኮሞ ቲቪ ሄሊኮፕተር

መጋቢት 8 የማሌዢያ አየርመንገድ አውሮፕላን

የካቲት 26 የማኦይ አየርመንገድ አውሮፕላን

የካቲት 21 የሊቢያ ኤር ካርጎ አውሮፕላን

የካቲት 16 የኔፓል አየር መንገድ አውሮፕላን

ጥር 20 የስኳላ ሱፐርየራ ዲ አቪየቴ ሲልቫ አውሮፕላን

ጥር 18 የትራንስ ጉያና አየር መንገድ አውሮፕላን

Published in ከአለም ዙሪያ
Page 3 of 16